Items filtered by date: Monday, 01 January 2018

የቢቢሲ የወሬ ምንጭ በድረ ገጹ ባስነበበው ዘገባ ባለፉት 12 ወራት ማለት ከፈረንጆቹ 2017 መባቻ እስከ መገባደጃው በርካታ ክስተቶች ዓለምን ጎብኝተዋል።  ከበርካታ ክስተቶች በጥቂቱ ከቁጥሮች ጋር አያይዞ ያቀረበ ሲሆን

37ሺ993 ቦምቦችና ሚሳዔሎች

ከጥር እስከ ጥቅምት ባለው ጊዜ በአሜሪካ የሚመራው ጥምር ኃይል ኢራቅ እና ሶሪያ ላይ የጣላቸው ቦምቦችና ሚሳዔሎች ብዛት37ሺ993 ደርሰዋል። ሩስያም በርካታ የጦር መሣሪያ በተጠቀሱት ቦታዎች ብታዘንብም  ቁጥሩ ይፋ አልተደረገም። ዋሽንግተን እና ሞስኮ በጥቃቱ የተጎዱ የሰላማዊ ዜጎች ቁጥር ብለው ካሳወቁት በላቀ ደረጃ ሰው ተጎድቷል ቢባልም ተልዕኮው አይ ኤስን ከሞላ ጎደል ከኢራቅና ሶርያ አስወጥቷል።

127እሣተ ገሞራ

የተጠቀሰውን ቁጥር ያህል ንቁ እሣተ ገሞራ በኢንዶኔዥያ ይገኛል። ይህም ሃገሪቱን በዓለማችን በርካታ የእሣተ ገሞራዎች ያሉባት ሃገር ያደርጋታል። ወርሃ ኅዳር ላይ ከእሣተ ገሞራዎቹ አንዱ ፈንድቶ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል።

1ነጥብ7 ሚሊዮን በአለም ላይ «እኔም» በሚል መሪ ቃል  ፆታዊ ጥቃትን

ያወገዙ ሰዎች

በአሜሪካው የፊልም ዓለም «ሆሊውድ» እየተከናወነ ያለውን ፆታዊ ጥቃት በመቃወም «me too» የተሰኘውን ቃል በመጠቀም የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻውን የተቀላቀሉ ሰዎች ቁጥር 1ነጥብ7 ሚሊዮን ደርሷል። በሃገራችን ኢትዮጵያም «እኔም» በሚል መሪ ቃል በርካቶች ፆታዊ ጥቃትን ሲያወግዙ ተስተውለዋል። ቢያንስ በ85 ሃገራት የሚገኙ ሴቶች በማህበራዊ ሚዲያው ዘመቻ መሳተፋቸው ተነግሯል።

ሐሰተኛ ዜና

በሰላም ዘርፍ የኖቤል ሽልማት ተሸላሚዋ የበርማ መሪ ኦንግ ሳን ሱ ኪ በማይናማር ያሉ የሮሂንጃ ሙስሊሞች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ያወገዙበት ክስተት። ምንም እንኳ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መሪዋ በሃገራቸው እየተከናወነ ያለውን ድርጊት እንዲያወግዙ ተፅዕኖ ቢያሳድርባቸውም፤ ሳን ሱ ኪ ይህን ሊያደርጉ አልቻሉም። ይልቁንም ሁኔታውን «ሐሰተኛ ዜና» ሲሉ አጣጥለውታል። የዓለም አቀፉ ድንበር የለሽ ኃኪሞች ማህበር በ2017 ብቻ 6 ሺህ የሚሆኑ የሮሂንጃ ሙስሊሞች መገደላቸውን ዘግቧል።

812 የእግር ኳስ ሜዳዎች

በፈረንጆቹ 2017 ሐምሌ ወር ላይ ከአንታርክቲክ ላይ የተደረመሰው የበረዶ ግግር። የበረዶ ግግሩ በእግር ኳስ ሜዳ ቢታሰብ 12 የዓለም ዋንጫዎችን በአንድ ጊዜ ማጫወት የሚችል ስፋት ያለው ይሆን ነበር። ሳይንቲስቶች ክስተቱ እየጨመረ ካለው የዓለም ሙቀት መጠን ጋር ተያያዥነት እንዳለው ይናገራሉ።

44 ጊዜ በየቀኑ

ከህንዷ ኒው ደልሂ የሚወጣው ጭስን መተንፈስ በቀን 44 ሲጋራ ከማጨስ ጋር እኩል ነው ሲሉ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ። በዓለም ላይ ካሉ 20 በጣም የተበከሉ ከተሞች መካከል አስሩ በህንድ ይገኛሉ።

60 ሚሊዮን የኦሎምፒክ መዋኛ ገንዳ

ሃሪኬን ሃርቪይ የተሰኘው ዝናብ የቀላቀለ አውሎ ንፋስ 150 ትሪሊዮን ሊትር የሚለካ ውሃ በአሜሪካ ላይ ጥሏል። በነሐሴ ወር በሂዩስተን ቴክሳስ የጣለው ዝናብ ልኬት ከ60 ሚሊዮን የኦሎምፒክ መዋኛ ገንዳዎች ውሃ ጋር እኩል ነው። አንደ የኦሎምፒክ መዋኛ ገንዳ 50 ሜትር ርዝማኔና 25 ሜትር ስፋት ሲኖረው ጥልቀቱ 2 ሜትር ይለካል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

 

አብርሃም ተወልደ

Published in ዓለም አቀፍ
Monday, 01 January 2018 22:27

ተመድ በ2017

ተመድ እንደ እ.አ.አ 2017 አለም አቀፍ ሰላምና ጸጥታ ለማክበር እንዲሁም አለም አቀፋዊ አመራርን በቁርጠኝነት ለማሳካት ባደረገው ጥረት በርካታ ተለምዷዊና ያልተለመዱ ተግዳሮች ገጥመውታል፡፡ እነዚህ ፈታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም ቅሉ አብዛኛዎቹ የመንግስታቱ ድርጅት አባል አገራት የተሻለችና ደህንነቷ የተጠበቀች አለም ለመፍጠር ሰርተዋል፡፡

ሽብርተኝነትና አክራሪነት፣ የኒኩሌር ችግር ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችና፣ የስደተኞች ችግር፣ የአደገኛ መድሃኒቶች ዝውውር፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የሳይበር ደህንነትና ሌሎች በ2017 አለም አቀፍ ተግዳሮቶች  መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ሰሜን ኮሪያና የኒውክሌር ፍጥጫው

እ.አ.አ እየተገባደደ ባለው 2017 የሰሜን ኮሪያ የተለያዩ የኔኩሌር ነክና ተያያዥ ረዥም ርቀት ሚሳይሎችን ሙከራ ማድረጓ አለማችንን ውጥረት ውስጥ የከተተ ጉዳይ ነበር፡፡ የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ አንቶዮ ጉቴሬዝ ሰሜን ኮሪያ ከቀጣናውና ከአሜሪካ ጋር ገብታው የነበረው ወታደራዊ ፍጥጫ እንዳሳስባቸው ገልጸው ሁኔታው የአለማችን ሰላምና ጸጥታ አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዋና ጸሃፊው ማንኛውም ወታደራዊ እርምጃ አውዳሚ ሊሆን እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል፡፡ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ችግሩን ለማቃለል በሚቻልባቸው መንገዶች ለመወያየት በአመቱ ተደጋጋሚ አስቸኳይ ስብሰባዎችንም ጠርቷል፡፡

አለም አቀፍ የስደተኞች ጉዳይ

የተመድ ስታትስቲክስ እንደሚያሳየው በአለም ዓቀፍ ደረጃ 65 ነጥብ6 ሚሊዮን ህዝበች ቀያቸውን ጥለው ተፈናቅለዋል፡፡ 22ነጥብ5 ሚሊዮን ከሚሆኑ ስደተኞች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከ18 አመት በታች ናቸው፡፡ 10 ሚሊዮን ሰዎችም ዜግነት የተከለከሉ እንዲሁም እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ የመቀጠርና በነጻነት የመንቀሳቀስ የመሳሰሉት መብቶቻቸው የተገደቡባቸው ናቸው፡፡

በአለም ላይ በግጭትና ስደት ምክንያት በየደቂቃው 20  ሰዎች እንደሚፈናቀሉም የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ኤጄንሲ መረጃ ያመለክታል፡፡ 2017 በድህነትና ግጭት ምክንያት ከሰሃራ በታች  100 ሺህ የሚጠጉ ስደተኞች የሜዲትራንያን ባህርን አቋርጠዋል፤ ከ3ሺህ በላይ ሰጥመዋል ተብሏል፡፡

ሊቢያ ደግሞ ሜድትራኒያንን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ሊሻገሩ የነበሩ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካዊያን ስደተኞች በባርነት ግዞት እስከመቅረብ የደረሱበት ዓመት መሆኑ ተሰምቷል፡፡

ግጭት፣ ጦርነትና ርሃብ

በመካከለኛው ምስራቅ፣ በሩቅ ምስራቅና በአፍሪካ አገራት የተነሱ ግጭቶች በርካቶችን ለሞት፣ ለቁስለት፣ ስደትና ርሃብ እንዲዳረጉ በር ከፍቷል፡፡ የመንን እያመሳት ያለው ጦርነት አገሪቱን አለች ከማትባልበት ደረጃ አድርሷታል፡፡

በዘመናዊው አለም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በየመንም 8ነጥብ5 ሚሊዮን ሰዎች ለከፋ ርሃብ ተጋልጠዋል፡፡ ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ንፁህና የመጠበቂያ ስርዓቶች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ወድመው ዜጎቿ በኮሌራ እንዲሞቱ ምክንያት ሆኗል፡፡ በየመን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያና ናይጄሪያ በተቀሰቀሰው ግጭት ዜጎቻቸው ለረሃብ የተጋለጡባቸው አገራት ሆነዋል፡፡

በሶርያ ባለፉት ሰድስት አመታት በተቀሰቀሰው ግጭት ከ250 ሺህ ሰዎች በላይ ሞተዋል፤ አምስት ሚሊዮን ደግሞ ተፈናቅለዋል፡፡ በማይናማር ደግሞ በአጭር ጊዜ አለማችን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች አገር ጥለው እንዲሰደዱ የሆነበት አስከፊ ዓመት ነበር፡፡

በአለም ደረጃ 130 ሚሊዮን ልጃገረዶችም ወደ ትምህርት ቤት እየሄዱ አለመሆኑ ለአለም መርዶ የተነገረበት ዓመት ይኸው ተሰናባቹ ዓመት ነበር፡፡

ልዩ ልዩ እምርታዎች

በአሜሪካ ክፍለ አህጉር የተከሰተው ንፋስ አዘል ወጀብ አውሎ ንፋስ ባልተለመደ መልኩ በርካታ ውድመት ጥሎ አልፏል፡፡ ይህም የአየር ንብረት ለውጥ አሳማኝ ተፈጥሯዊ ማስረጃ ሆኖ የቀረበበትና የፓሪሱ የአየር ንብረት ስምምነት ወደ ተግባር እንዲገባ ተመራማሪች ጥሪ ያቀረቡበት ጊዜም ነው፡፡

ቻይናም በተጠናቀቀው በዚህ ዓመት በተመድ ውስጥ ያላት ተሰሚነት እየጎላ መምጣቱና በማደግ ላይ ያሉ አገራት አሳሳቢ ጉዳዮች ሁሉ ወደ ጠረጴዛ እንዲቀርቡ ቁልፍ ምዕራፍ የተከፈተበት ዓመት ሆኖ ተመዝገቧል፡፡

ተመድና የአንድ ዓመት መሪው

ገና የአንድ ዓመት የስልጣን ጊዜ ያሳለፉትና የባንኪ ሙንን እግር ተክተው የተመድ ሁነኛ ሰው የሆኑት አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በመላው ዓለም ሰላምና ፍትህ እንዲሁም ልማት ጭምር እንዲሰፍን ተንቀሳቅሰዋል ፡፡ይሁን እንጂ አሁንም የ2017 ሁነኛ ተግዳሮቶች ሆነው የተሻገሩት የቤት ስራዎች ተፈተው የተሻለች ዓለምን ለመፍጠር በርካታ የቤት ስራዎች ከፊታቸው ተደቅኗል፡፡

በእርግጥ ዓለም በተለይም አብዛኛው የተመድ አባል አገራት በኮሪያ ልሳነ ምድር ላይ በነገሰው የኒውክለር ውጥረት፣ በአየር ንብረት ለውጥ አሳሳቢነት ላይ ፣ ሽብርተኝነትን በመዋጋትና መፍትሄ ባላገኙ የአለም ሌሎች ችግሮች ላይ መተባበር ማሳየታው ለድርጅቱ መልካም ተስፋዎች ቢሆኑም፤  ልዩነቶችን አስታርቆ ለእልባት መትጋትና ለተሻለች አለም ጉቴሬዝ በ2018ም የሚፈተኑ ሆነው ይዘልቃሉ፡፡

ምንጭ፦ዥንዋ፣ የተመድ ዜና ማዕከልና ኢቢሲ

አብርሃም ተወልደ

 

Published in ዓለም አቀፍ

ከህብረ ብሄራዊነት ዋነኛ መገለጫዎች መካክል የብሄር፣ የቋንቋ፣ የሀይማኖት እና የባህል ብዝሃነት ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ብዝሃነት ነባራዊ ሁኔታ ነው። በህብረብሄራዊ የፌዴራል ስርዓት ውስጥ  ብዝሃነትን ማክበር መሰረታዊ ጉዳይ ነው።ልዩነቶችን በሚያስተናግድ ሥርዓት ውስጥ  ብዝሃነት ከህብረብሄራዊ ውበትነት አልፎ የስርዓቱ ምሰሶ ሆኖ በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነት እንደሚያጠናክር የመስኩ ተንታኞች ይስማሙበታል፡፡

«ብዝሃነት ማለት መቻቻል ማለት ብቻ ሳይሆን ልዩነቶች በፈጠሩት እሴቶች እና ለልዩነታችን መኖር ምክንያት በሆኑ ማንነቶች ላይ መግባባት እና የጋራ ግንዛቤ (መረዳዳትን) መፍጠር ነው» በማለት የሚያስረዱት የመስኩ ተንታኞች፤ መቻቻል ለአብሮነት የሚያስፈልግ የጋራ እሴት ቢሆንም ተቻችሎ ለመኖር ግን አንዱ የሌላውን እምነት ምንነት እና ማንነት በጥልቀት ማወቅ አስገዳጅ   ባይሆንም ማክበር የግድ ነው።

በአገራችን  የፌዴራል ስርዓት ከሰፈነ ዓመታት ቢቆጠሩም ዜጎች በህገ መንግስቱና በስርዓቱ ምንነት ላይ ያላቸው ግንዛቤ በሚፈለገው ደረጃ  ላይ እንዳልደረሰ ይታመናል። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከተለያዩ ክልሎች የሚሰባሰቡና የሀገሪቱን ህዝቦች የሚወክሉ እንደመሆናቸው መጠን በብዝሃነት ላይ ብቻ ሳይሆን የራሳቸውን ማንነት በሚገባ እንዲገነዘቡና ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር እሴትን እንዲያዳብሩ  ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል። ተማሪዎች የቋንቋ፣ የባህልና የሃይማኖት ልዩነትን የማክበር ልምድን በማዳበር፤ በመማር ማስተማር ሥራው እርስ በርስ እንዲደጋገፉ በስነ ምግባር የማነፁ ሃላፊነት የዩኒቨርሲቲዎቹ  መሆን አለበት።

 የመቻቻል እሴት በሀገራችን ህዝቦችና ሃይማኖቶች ፅኑ መሠረት የያዘ፣ በፌዴራል ስርዓቱ ዕውቅናና ዘላቂ ዋስትና የተሰጠው እሴት ነው። የሀገር ዕድገት፣ ብልፅግናና ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው የፌዴራል ስርዓቱን በማጠናከር፣ የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በማረጋገጥና ለዘመናት ዘልቆ የቆየውን የመከባበርና የመቻቻል እሴት በማጉላት  መሆኑ አይካድም።

ቀደምት አባቶቻችን ያቆዩትን ተሳስቦና ተከባብሮ የመኖር ባህል ለማጎልበትና ለመጭው ትውልድ ለማስተላለፍ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ምሁራን አርአያ በመሆን ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል። በህገ መንግስቱ የተከበሩ የህዝቦች እኩልነት መብቶች በአግባቡ እንዲተገበሩና ልዩነቶች የግጭት መንስኤ ሳይሆን የመቻቻልና የአብሮነት ባህል እንዲጎለብት ለማድረግ መስራት ለነገ የሚተው ጉዳይ ሊሆን አይገባም።

በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለውን ልማት ለማስቀጠልና የህዝቦችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ መቻቻልና ዘላቂ ሠላምን ማረጋገጥ የሁሉም ዜጎች ኃላፊነት ሊሆን ይገባል። በፌዴራል ስርዓቱ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ማንነታቸው በመከበሩ በቋንቋ የመማርና የመዳኘት፣ ባህልና ታሪክን የማሳደግ ዕድል  በማግኘታቸው ሊኮሩ ይገባል። ይህን የእኩልነት መንፈስ በማጠናከር ለመጭው ትውልድ የበለፀገችና አስተማማኝ ሰላም የተጎናፀፈችዋን ኢትዮጵያ ማስተላለፍ ይገባል።

 የዜጎች እኩልነትን ማሳያዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሆናቸው ሊዘነጋ አይገባም። ምክንያቱም የወደኋላ ታሪካችንን ብንቃኝው በጥቂት ዩኒቨርሲቲዎች የመማር እድል የሚኖራቸው ጥቂት ዜጎች ብቻ  እንደነበሩ መዘንጋት አይገባም። ዛሬ በሁሉም ክልሎች 44ዩኒቨርሲቲዎች ተከፍተው በርካታ ዜጎችን በማስተማር ላይ ናቸው። ለዚህም ነው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዛሬዋ ኢትዮጵያ ማሳያ ነፀብራቆች ናቸው የሚባለው። ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በአንድ ላይ የሚገኙባቸው ተቋማት በመሆናቸው ህብረ ብሄራዊነት ይበልጥ ሊንፀባረቅባቸው ይገባል እንጂ የግጭት አውድማ ሊሆኑ አይገባም።

ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ በተማሪዎች መካከል ብሄርንና ማንነትን መሰረት አድርገው በሚነሱ ግጭቶች በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።  ንብረት ወድሟል። ይህ ክስተት የመማር ማስተማር ሂደቱን ከማስተጓጎሉም ባሻገር ጥቂት የማይባሉ ተማሪዎች ለደህንነታቸው በመስጋት ወደየመጡበት በመመለስ ተጉላልተዋል። ትምህርታቸውን ለማቋረጥም የሚወስኑ እንደሚኖሩ ይታሰባል። ብዙዎቹ ደግሞ ስጋት ውስጥ ሆነው ባልተረጋጋ መንፈስ በመማር ላይ ይገኛሉ።

መንግሥት ነገሩን ለማረጋጋት በትምህርት ተቋማቱ ውስጥ የፀጥታ ኃይሎችን ከማሰማራቱ በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲዎቹ የሰዓት እላፊ ገደብ ለመጣል ተገዷል። በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎች ከመንግሥት አካላትና በየአካባቢው ካሉ የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ውይይት በማድረግ ላይ ናቸው።

የክፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፌዴራሊዝም ስርዓትን ምንነትን በገቢር ሊያሳዩ ይገባል። ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በማንነታቸው እንዲኮሩ፣ ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውንና ታሪካቸውን እንዲያሳድጉ እንዲሁም ማህበራዊ እሴቶቻቸውን ለማበልፀግና እርስ በርስ ተከባብረው ለመኖር የሚያግዙ መሆን ይገባቸዋል።

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሃገሪቱን ህገ መንግስትና የፌዴራል ስርዓቱን በሚገባ እንዲያውቁ በትኩረት መስራት የግድ ይላል። በተለይም አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገው ርብርብ ግቡን እንዲመታ ተማሪዎች የህብረብሔራዊ አንድነትን  እውቀት ማሳደግ ይገባል።

Published in ርዕሰ አንቀፅ

አዲስ አበባ፡- በትግራይ ክልል ሐገረ ሰላም እና በአሸጎዳ ንፋስ ኃይል ማመንጫ አካባቢዎች ለተለያዩ የኃይል አቅርቦቶች የሚውል ተጨማሪ የንፋስ ኃይል መኖሩ በጥናት መረጋገጡን የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ቡድን አስታወቀ።

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሜካኒካል ምህንድስና መምህር እና የታዳሽ ኃይል ተመራማሪው ተባባሪ ፕሮፌሰር ሙሉ ባይራይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በትግራይ ክልል የንፋስ ኃይል እምቅ ሀብትን ለመመርመር የሚያስችል ጥናት በዩኒቨርሲቲው አማካኝነት ተካሂዷል። አንድ የምርምር ቡድን ተዋቅሮ በተካሄደው ጥናት መሰረት በሐገረ ሰላም አካባቢ የንፋስ ኃይልን ተጠቅሞ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል ከፍተኛ የንፋስ ሃይል መኖሩ ተረጋግጧል። በሃገረ ሰላም ከፍተኛ ቦታዎች ላይ በተደረገው ጥናት በአመት በአማካይ 6 ነጥብ 96 ሜትር በሰከንድ ፍጥነት ያለው ነፋስ እንዳለ ለማወቅ ተችሏል።

እንደ ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉ ገለፃ፤ ጥናቱ በመቀሌ፣ በአሸጎዳ፣ በሐገረ ሰላም እና በሌሎች የትግራይ አካባቢዎች ላይ መደረጉን አስታውሰው፤ ከመሬት በላይ 30 ሜትር የሚደርሱ የንፋስ ፍጥነት መለኪያ መሳሪያዎች ጥቅም ላይ ውለዋል። በሐገረ ሰላም የተገኘው ውጤትም በዘርፉ ለቀጣይ ጥናት እና ምርምር የሚጋብዝ ሲሆን፤  በአሸጎዳ በተደረገው ጥናት አሁን ጥቅም ላይ ከዋለው የንፋስ ሃይል ማመንጫ በተጨማሪ በአካባቢው ማስፋፊያዎች አካሂዶ ተጨማሪ ኃይል ማግኘት እንደሚቻል ያሳየ ነው።

የአሸጎዳ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ኤሌክትሪክ እያመነጨ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው ጥናት መሰረት በአካባቢው ተጨማሪ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል ሀብት  መኖሩ ተረጋግጧል። በአሸጎዳ ያለው የንፋስ ኃይል ማመንጫ ቀድሞ በተሰራው ጥናት መሰረት የንፋሱ ፍጥነት በአመት በአማካይ ሰባት ነጥብ ሁለት ሜትር በሰከንድ እንደሚደ ርስም ጠቁመዋል።

በቦታዎቹ ላይ ያለውን የንፋስ ኃይል ተጠቅሞ ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ዝርዝር ጥናት ያስፈልጋል የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉ፤ የእምቅ ንፋስ ኃይሉን ጥናት መሰረት በማድረግ ዝርዝር ጥናቶች በቀጣይ መከናወን እንዳለባቸው አስታውሰው፤ በሐገረ ሰላም እና በአሸጎዳ ማስፋፊያ ላይ የቦታ መረጣ እና የተስማሚነት ጥናቶችን በማካሄድ ለአገሪቷ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚቻልበት እድል መኖሩ ተናግረዋል።

ጥናቱ የተካሄደው በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ድጋፍ አማካኝነት ሲሆን፤  ከሁለት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይፋ በተደረገው የምርምር ፕሮጀክቶች  ላይ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ ሽግግር የአነስተኛ ነፋስ ኃይል ማመንጫ ተርባይን ቴክኖሎጂ ምርምር ስራ በመመረጡ ነው። በኢትዮጵያ በአሸጎዳ 120 ሜጋ ዋት በተጨማሪ አዳማ አንድ እና ሁለት የንፋስ ኃይል ማመንጫ 204 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት መቻሉ ይታወሳል።

ጌትነት ተስፋማርያም

 

Published in የሀገር ውስጥ

 ኢትዮጵያና ኤርትራ  ወደ ጦርነት ከገቡ ጀምሮ ላለፉት 20 ዓመታት የመንግሥት እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች ተቋርጦ ቆይቷል። በሁለቱም ሀገራት መካከል ጦርነትም ሆነ  ሰላም እንደሌለ ይነገራል። ይሁን እንጂ ህዝቦች መካከል የነበረውን መራራቅ ለማቀራረብ ግለሰቦች ሥራ ጀምረዋል። የሀገራቱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች መጠናከር ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ምን ፋይዳ ይኖረዋል? በሚለው ጉዳይ ላይ የተለያዩ ሃሳቦች ይነሳሉ። በርግጥ  የህዝብ ለህዝብ  ግንኙነቱ ተስፋ ይኖረው ይሆን?

አቶ አብርሃም ገብረሊባኖስ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ለማስጀመር የተነሱ ግለሰብ ናቸው። እርሳቸው እና አቶ ሀብቶብ ገብረሊባኖስ በጋራ የአገራቱን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በተመለከተ በአዲስ አበባ ምሁራንን ያሳተፈ የፓናል ውይይት አዘጋጅተው ነበር። ለዚህ  ባለፈም ወደፊት የተጠናከረ ሥራ ለመሥራት አቅደዋል።

እንደ አቶ አብርሃም ማብራሪያ፤ የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ወደነበረበት ለመመለስ ላለፉት ሃያ አመታት ለመንግሥታቱ በመተው ውጤት አልመጣም። የግጭቱ ዋነኛ ተጎጂ የሆኑት ደግሞ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች በመሆናቸው ሰላማዊ ግንኙነቱን መቋረጥ አይገባማ ይላሉ። ምክንያቱንም ሲገልፁ፤ ከጦርነቱ ወዲህ የሁለቱ አገራት ህዝቦች አንዱ ወደ አንዱ መኖሪያ አካባቢ በነጻነት ተዘዋውሮ እንዳይኖሩ አግዶታል። በመሆኑም በቀጣይ የመንግሥታቱን ችግር ወደ ጎን በመተው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ መሥራት ይገባል። እርስ በእርሳቸውም በመደጋገፍ መጠቀም የሚችሉት ሀብት እየባከነ በመሆኑ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ማጠናከር እንደሚገባ ይናገራሉ። 

ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ህዝቦች ቀድሞም ቢሆን ወዳጅ ናቸው። ተመሳሳይ ባህልና ሃይማኖቶች ያላቸው ከመሆናቸውም በላይ በታሪክ አንድ የነበሩ ናቸው። በመጥፎ የፖለቲካ አጋጣሚ አንድ ህዝብ ሆነው ሁለት ሀገር ለመሆን መገደዳቸውን ይናገራሉ። በመሆኑም በድንበር አካባቢ በተነሳው ግጭት ምክንያት ህዝቦች ተለያይተው መቅረት የለባቸውም። በሁለቱም አገራት ያሉ ባለሥልጣናት ከጦርነቱ በፊትም እርስ በእርስ  በቅርበት የሚተዋወቁ በመሆናቸውና  ወደ በጎ አቅጣጫ ለመመለስ ተቸግረዋል። አሁን ግን በአገራቱ ያለው ትውልድ አዲስ በመሆኑና የቀደመውን የቡድንም ሆነ የግለሰቦች ቁርሾ የማያግደው በመሆኑ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን እንደገና ማስቀጠል ይቻላል። የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ወደነበረበት ለመመለስ የሚደረገው ጥረት ዘግይቷል የሚያስብል ቢሆንም፤ በቀጣይ ተጠናክሮ መካሄድ  እንደሚገባው ይጠቁማሉ።

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር የማነ ዘርአይ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ አስፈላጊ ነው የሚለውን የአቶ ልደቱ እና አቶ አብርሃምን ሃሳብ ይጋራሉ። በድንበር ኩታ ገጠም የሆኑ አገራት ያላቸው የህዝቦች ግንኙነት ኩታ ገጠም ካልሆኑት የተሻለ መሆን ይገባዋል። ነገር ግን ከዓመታት በፊት የተከሰተው ጦርነት በህዝቦች ግንኙነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ፈጥሮ ቆይቷል። ሆኖም ግን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ የተቆራረጠ መሆን እንደሌለበት ያምናሉ።

በጦርነቱ ምክንያት የተፈጠረውን የህዝቦችመለያየት ተከትሎ በድንበር አካባቢዎች ላይ ወታደሮች ሰፍረዋል። በዚህም ነጻ የህዝቦች ግንኙነት ተቋርጦ ቢቆይም ከኤርትራ በርካታ ሰዎች በየጊዜው እየፈለሱ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ። በውጭ አገራት የሚኖሩ የሁለቱ አገራት ህዝቦች ከሌሎች አገራት ህዝቦች ጋር ከሚኖራቸው ግንኙነት ይልቅ እርስ በእርስ የመቀራረብ ልምድ አላቸው። በሁለቱ አገራት ዜጎች በሚዘጋጁ የኪነጥበብ ሥራዎች ላይም እየተሳተፉ አንዱ የአንዱን ሙዚቃ እና ባህል ይለዋወጣሉ። አሁን የተጀመረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲኖር ግፊት የማድረግ ጥረት በአንድ ጊዜ የመጣ ሳይሆን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገራት ያለው የህዝቦቹ መስተጋብር ማየል ያስከተለው መሆኑን ይናገራሉ።

እንደ አቶ አብርሃም ገለጻ፤ ከሁለቱም ወገን በተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም አርቲስቶች የሚሳተፉባቸው የተለያዩ መወያያ መድረኮች፤ የባህል ልውውጥን የሚያበረታቱ ዝግጅቶችን ማካሄድ ያስፈልጋል። ሥራው በጥናታዊ ጽሁፎች ላይ በተመሰረተ ውይይት ቀደም ብሎ በአዲስ አበባ ተጀምሯል፤ በቀጣይ በኤርትራም ህዝቦችን በማስተባበር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ አስፈላጊነትን የሚያሰርጹ መድረኮች መካሄድ አለባቸው። ከሁለቱም ሀገራት የተለያዩ የህብረተሰብ ከፍሎች የተውጣጡ ተወካዮች በጋራ ኮሚቴ አዋቅረው መንግሥታቱ ላይ ወደ ሰላም እንዲመጡ ጫና መፍጠር ይገባቸዋል። በመሆኑም ህዝቦቹን በማቀራረብ ለጋራ ችግሮቻቸው መፍትሄ እንዲሰጡ በማድረግ መንግሥታቱ ላይ በጎ ተጽእኖ መፍጠር ይቻላል።            

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱም እየተጠናከረ በመጣ ቁጥር ወዳጅነቱ ስለሚያይል የሁለቱ መንግሥታት ላይ ግፊት ለማድረግ ያስችላል። ግንኙነቱ እውን መሆኑ በዋነኛነት መንግሥታቱ ላይ በጎ ጫና በማሳደር በአገራቱ መካከል ሰፍኖ የቆየውን ጥርጣሬ በመፋቅ ሰላማዊ ቀጣና እንዲሰፍን ይረዳል። የሰላማዊ ቀጣና መኖሩ ደግሞ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ያለውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው፤ የህዝብ ለህዝቡ ግንኙነት መንግሥታት ላይ ግፊት ለማድረግ ያስችላል  ከሚለው የአቶ አብርሃም ሃሳብ ይልቅ፤ ሁለቱን መንግሥታት ስለጉዳዩ አሳምኖ ተቀባይነት እንዲያገኝ ማድረግ ለውጤታማነቱ ቁልፍ መሆኑን ይናገራሉ። የማሳመኑ ጥረትም ድካም የሚጠይቅ ቢሆንም መንግሥታቱ ካመኑበት ደግሞ ህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ በቀጣይ ውጤታማ እንደሚሆን ይገልፃሉ።

መንግሥታቱ በጉዳዩ ላይ ካላመኑበት አላመኑበትም ብሎ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ እንደማይገባ የሚናገሩት አቶ ልደቱ፤ የተቻለውን ያህል የማሳመን ጥረት እያደረጉ መቆየት ለህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማሳካት ወሳኝ ነው። የህዝቦቹ ግንኙነትም ለአገራቱ የጋራ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጥቅም ያስገኛል። ሰላም ከተፈጠረ ለአብነት ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብን በመጠቀም የወደብ አማራጮቿን የማስፋት እድል ስታገኝ ኤርትራ በበኩሏ ወደቡን በማከራየት ማግኘት የሚገባትን ገቢ ታገኛለች።

የኢትዮጵያም ሆነ የኤርትራ ህዝቦች ከኢኮኖሚው ባለፈ በጋራ በሚኖራቸው መስተጋብር ዘርፈ ብዙ የማህበራዊ ትስስትርና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ይኖራቸዋል። በፖለቲካው ዘርፍ ሰላም ሲፈጠር እና ህዝቦች ሲቀራረቡ በየጊዜው ሊፈጠሩ የሚችሉ የፖለቲካ አለመግባባቶችን እና የድንበር ግጭቶችን በቀላሉ ለመፍታት እድሉ ይሰፋል ይላሉ።

ረዳት ፕሮፌሰር የማነ ደግሞ፤ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው ማድረግ ይገባል የሚል ከሁለቱ ምሁራን የተለየ ሃሳብ ያቀርባሉ። በተለይም ግንኙነቱ በአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድጋፍ እንዲኖረው ማድረግ ግንኙነቱ ውጤታማ እንዲሆን ያግዛል። በመሆኑም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ መጠናከር በዋናነት ዓለም አቀፋዊ ተቋማት እና እንደ አሜሪካ ያሉ ተጽእኖ ፈጣሪ አገራት እንዲሳተፉበት ማድረግ እንደሚገባም ይገልጻሉ።

እንደ አቶ አብርሃም እምነት ከሆነ፤ አገራቱ በድንበር አካባቢ ጦራቸውን በማስፈራቸው ከአንዱ አገር ወደ ሌላው በነፃነት የመንቀሳቀስ እድሉ ተገድቧል። በኢትዮጵያ በኩል ሰናፌ ላይ መድፍ ተደቅኖ ዛላአንበሳ ወይም አዲግራት ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስ ለኢንቨስተሮች ስጋት ይፈጠራል። በኢትዮጵያ በኩል የጦር መሳሪያ በተጠንቀቅ ተዘጋጅቶ  በኤርትራ ለሚሠማሩ ባለሀብቶች መተማመኛ አይፈጥርም።

«የሰላም ተጽእኖው በኢኮኖሚው ላይም አሉታዊ ተጽእኖ እየፈጠረ መቀጠሉን መገንዘብ ያስፈልጋል» የሚሉት አቶ አብርሃም፤ በተለያዩ አገራት የሚኖሩና በየአገራቱ ያሉ ዜጎችን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በበጎ በመመልከት ለሰላም ውጤቱ ስኬት መጣር ይገባቸዋል። ነገር ግን ጉዳዩን ለመንግሥታቱ ብቻ የሚተው ከሆነ ችግሮች እየተንከባለሉ እንዲቀጥሉ ያደርጋል። በተለይ  በህዝቦች ግንኙነት ሊፈጠር የሚችለውን ሰላም ተጠቅሞ ሊሳኩ የሚችሉ የፖለቲካ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ዜጎች እንዳያገኙ መንገድ እንደሚዘጋ ይናገራሉ።

አቶ ልደቱ ደግሞ፤ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ይቅር ብሎ መቀመጥ እና ህዝቦች የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው እንዳይጠናከር ከተደረገ የሁለቱም ህዝቦች ሊያገኙ የሚገባቸውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጥቅሞች እንደመከልከል ይቆጠራል። በመዘግየቱም  ሊጎዱ የሚችሉት የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ሊሆኑ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ። 

የረዳት ፕሮፌሰር የማነ ስጋት ደግሞ፤ መንግሥታት ይቀያየራሉ ነገር ግን ቋሚ የሚሆነው ህዝቡ ነው። የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ሲጠናከርም ዜጎቹ ሰላምን በነፃነት በማጣጣም ፊታቸውን ወደ ልማት ብቻ እንዲያዞሩ ያደርጋል። ግንኙነቱን ማጠናከር ካልተቻለ ግን በትብብር ሊሠሩ የሚገባቸውን የሰላም ሥራዎች በውጤታማነት ለማከናወን እክል ይፈጠራል።

ዜና ትንታኔ

ጌትነት ተስፋማርያም

Published in የሀገር ውስጥ

ዕለቱ ረዕቡ ነው። ሰዓቱም ወደ እኩለ ቀን ተቃርቧል። የቀጠሮዬ ቦታ እንደደረስኩ የማነጋግራቸውን ሰዎች የነገሩኝና ቀጠሮ የያዙልኝን ሰው ከተወሰኑ አዛውንቶች መሀል ቁጭ ብለው አገኘኋቸው። ሰላምታ ተለዋውጠንም ወደ አንዱ ክፍል ዘልቄ እንድገባ አቅጣጫውን በእጃቸው ጠቆሙኝ። እንዴት ዋላችሁ! ደህና ናችሁ! የሚል ሰላምታ እያቀረብኩም ግራና ቀኝ ባሉት አልጋዎች መካከል አለፍኩ። ገሚሶቹ በአልጋቸው ላይ እንደተኙ እንቅልፍ አሸልቧቸዋል።

 የተወሰኑት ደግሞ ብርድ ልብሳቸውን ተከናንበው አልጋቸው ላይ ቁጭ ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ የጸሐይ ሙቀት ለማግኘት ወጥተዋል። ቁስላቸው እየመዘመዘ አላስተኛ ሲላቸው የሚያቃስቱም ነበሩ። ድንገት ዝግ ባለና በደከመ ድምጽ ፈጣሪ አይዞሽ ይበልሽ! የሚል ድምጽ ጆሮዬ ደረሰ። ፊቴን ድምጹን ወደሰማሁበት መለስ አደረግሁ። በግምት 50ዎቹ እድሜ ላይ የሚደርሱ አዛውንት ናቸው። በወደቁትን አንሱ መርጃ ማህበር ብርድ ልብሳቸውን እንደለበሱ አልጋቸው ላይ ጋደም ብለዋል ።

አጠገባቸው እንደደረስኩ «እኔ ዘፋኝ ነበርኩ። በፖሊስ ኦልኬስትራ ሱዳንኛና አማርኛ ዘፈኖችን እጫወታለሁ። አሁን እንዲህ ሆኜ ቁጭ ብያለሁ። ይኸው ፈርሃ እግዚአብሔር ያለው ሰው እዚህ እኛን ሰበሰበን» አሉኝ። ሁኔታቸው አሳዝኖኝ አጠገባችው ቁጭ አልኩና ማዳመጤን ቀጠልኩ። አስጎብኝየም የምፈልጋቸው ሰው እርሳቸው እንደነበሩ አወጋኝና ሌላ ሥራ ስላለበት ወደ መጣበት አመራ።

እኔም በወጉ ከእርሳቸው ጋር ለመነጋገር እራሴን አዘጋጀሁ። የስራ ባልደረቦቼም በዚያው ተቀመጡና በሚገባ ታሪካቸውን እንዲያወሩን ጠየኳቸው። እርሳቸውም በሚገባ ህይወታቸውን እንደሚያጫውቱኝ ፈቃደኝነታቸውን ሰጡኝና ንግግራቸውን ቀጠሉ። አዛውንቱ አርቲስት መኮንን ሽፈራው ይባላሉ። ብዙ ህይወታቸውን በስፋት አጫውተውናልና ከተሞክሯቸው ትንሽ ተማሩ አልን። መልካም ንባብ።

በፈተና የታጀበ ልጅነት

ውልደትና እድገታቸው በአሁኑ ደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሆሳዕና ከተማ ውስጥ ነው። በልደት ካርድ የተረጋገጠ ትክክለኛ ዕድሜያቸውን ባያውቁትም ከቤተሰቦቻቸው እንደሰሙት በነሲብ ነው ጊዜው የሚነገራቸውና «በሸንቁጤው ጊዜ» ተወለድህ ይሏቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።«ሸንቁጤ» ማለትም የረሃቡ ዘመን እንደሆነም ነግረውኛል። እንግዳችን ወላጅ እናታቸውንና አባታቸው ገና በጨቅላነት እድሜ ላይ እያሉ በማያውቁት ምክንያት ይጣላሉ። ስለዚህም እንደ ዕድሜ እኩያ ልጆች ቦርቀውና ሮጠው እንዳያድጉ ሆነዋል፤ ከአንዱ ቤት አንዱ ቤት ሲሉም ኑሯቸውን ገፍተዋል። ይህ ደግሞ የልጅነት ጊዜያቸውን በእንጀራ እናት ቤት፣ በእንጀራ አባት ቤት፣ በአክስትና አጎት እንዲሁም በአያት ቤት እየተዘዋወሩ እንዲያሳልፉ አስገድዷ ቸዋል። ልጅነታቸውንም በሚገባ አጣጥመውት እንዳያሳልፉትም እንቅፏት ሆኖባቸው ነበር። የእንጀራ እናት ኑሮ ሰላም አልሰጣቸውም። አያታቸው ጋር ሄደውም ለመኖር የልጅ ልጆቻቸው አላስጠጋም ይሏቸው ነበር።

እንደውም እነዚህን የልጅ ልጆች ሲገልጿቸው  እንዲህ ነበር ያሉት። «የልጅ ልጅ እህል ፈጅ በኋላም ጅብ አስፈጅ» በማለት። ይህንን ያሉበት ምክንያትንም ሲያብራሩ የልጅ ልጆቹ አያታቸውን በተለያየ መልኩ ያሰቃይዋቸዋል፤የመሬትና የገንዘብ ድሃ እስኪሆኑ ድረስም በዝብዘዋቸዋል። በመጨረሻም በእነርሱ የእርስ በእርስ አለመስማማት ሳቢያ ህይወታቸው አልፏል። ይህ ደግሞ እርሳቸው እንዳይሳተፉበትና አያታቸውን እንዳያስቀይሙ በሚያደርጉት ግብግብ አማካኝነት የተፈጠረ እንደነበር አጫውተውናል። እናም ይህ ስቃይ  ስለከበዳቸው ወደሌላ ቦታ ማምራት ፈለጉና ጉዟቸውን ወደ አርሲ አደረጉ።

ባለታሪኩ እንግዳችን የተለየ ስጦታ ባለቤት ናቸው። ማለትም በዘፈንና የተለያዩ መጣጥፎችን በመጻፍ ይታወቃሉ። ስለዚህም ሲከፋቸውም ሆነ ሲደሰቱ ጨዋታቸውና እንጉርጉሯቸው ከወረቀትና ከድምጻቸው ጋር አደረጉ። በዚህ ድርጊታቸው ደግሞ ሁሉን ነገር ይረሱበታል። ታዲያ ይህ ባህላቸው አብሮ ተከትሏቸው ኖሮ በሄዱበት ስፍራ እውቅናንና የእንጀራ ሁኔታቸውን እንዲያደላድሉበት አስቻላቸው። ደስተኛ የሚሆኑበትን እድልም አቀዳጃቸው።

የትምህርት ህይወት

እንግዳችን መኮንን በጣምም ሀብታም በጣም ደግሞ ድሃ ከሆኑ ቤተሰብ ያልተወለዱ ልጅ ሲሆኑ፤ የመማር እድልን ለማግኘት በአንዱ ዙር መቀመጥ ያስፈልጋልና ብዙ ፈተናን አይተዋል። በወቅቱ ደግሞ በቅርብ የትምህርት እድል የሚያገኙበት ሁኔታ ስለሌለ ሳይማር ህይወቱን የሚመራው ሰው በርካታ ነበር። ይሁን እንጂ እርሳቸው ግን በዚህ ውስጥ አልነበሩም አመሻሽ ላይ ቢሆንም መማር ችለዋል። ነገር ግን እርሳቸውም ከእነዚህ ጎራ የሚመደቡ የሆኑበት አጋጣሚ ነበር። በእግራቸው ጭምር ረጅም መንገድ ጠፍተው ተጉዘው ባመጡት መፍትሄ ለመማር ችለዋል።

ከዚያ ግን በቅርባቸው በአያታቸው አነሳሽነት የአካባቢው ማህበረሰብ ባይወደውም በግዳጅ ዳስ እየሰራ ልጆቹን እንዲያስተምር ሆነ። ትምህርትን እንደ ጦር የሚፈራውና ዘመነኛ ነው ስለዚህ ባህላችንን ሊያጠፋ ተነስቷል በሚባልበት ጊዜ እርሳቸውና መሰሎቻቸው ለመማር ጓዛቸውን ጠቀለሉ። ማህበረሰቡ ባዘጋጀው ዳስ ውስጥም የዘመናዊ ትምህርትን ጣዕም ቀመሱት። ይህ ግን ከአያታቸው ዘንድ ሀሳቡ የሰረጸ ቢሆንም ሌሎች ቤተሰቦቻቸው በስፋት እንዲቃወሟቸውና እጃቸውን እንዲያነሱባቸው አደረጋቸው።

 ቀድመው በሌሎች አካባቢዎች እየተዘዋወሩ የተማሩ ስለነበሩ ደግሞ ማህበረሰቡም ቢሆን ሊገላቸው ያፈላልጋቸው ጀመር። ይህ ስጋት ደግሞ አባታቸውን በጣም አሳሰበ። ስለዚህም ከአካባቢው በድብቅ  እንዲሰወሩ ተደረጉ። በዚህ ምክንያት ደግሞ ትምህርታቸው ተቋረጠና ወደ አዲስ አበባ መጡ። የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወኑ እዚያ ካቆሙበት ትምህርታቸውን ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተብሎ በሚጠራው የዛሬው ኮተቤ ሜትሮፖሊታንት ዩኒቨርስቲ ውስጥ በመግባት ከዘጠነኛ እስከ 11ኛ ክፍል መማር ቻሉ።

ከዚያ በኋላ ግን ትምህርታቸውን አልቀጠሉም። ምክንያቱም ራሳቸውን በእራሳቸው እያስተዳደሩ ስለሚማሩ በአደጋ ውስጥ ወደቁ፤ የዲስክ መንሸራተት ገጠማቸው። አለሁልህ የሚል በሌለበት ወቅት ይህ መሆኑ ደግሞ እንኳን ትምህርትን ለመቀጠል ራስን አድኖ ወደነበረበት ለመመለስ ይከብዳል። ስለዚህም ትምህርቱ በዚህ ቆመ።

የጎዳና ኑሮ 

ከላይ እንዳልኩት ችግሩ ስለገጠማቸው በተለምዶ ፈረንሳይ ለጋሲዮን እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ብረት ድልድይ ዙሪያ በድልድዩ ላይ ሸራ በመከለል ከሦስት ዓመት በላይ ተቀመጡ። ምክንያቱ ደግሞ የሚያስጠጋ ወገን ዘመድ ስላልነበራቸው ዕጣ ፈንታቸው ያመጣው ነው። የዲስክ መንሸራተቱ ደግሞ እጅና እግራቸው ተሳስሮ እንደልብ መንቀሳቀስ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል። በሆስፒታል ለመታከም ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም። ስለማይንቀሳቀሱም በዚህ መጠለያቸው ጀርባቸው ከፍራሹ ጋር ተጣበቀ፣ እጅና እግራቸው ተሳስሮና ሰውነታቸው ሸቶ ጥቂት ወራት ተቆጠሩ።

 ራሳቸውን መከላከል ባለመቻላቸው አይጥ እግሮቻቸውን እስኪበላ ድረስ ድልድይ ውስጥ እንደወደቁ ውሃ እንኳ የሚያቀብላቸው አጥተው የመከራ ጊዜን አሳለፉ። አንዳንዴ ያው ለነብስ ያለና በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች አልፎ አልፎ የሚቀምሱት ነገር ይሰጧቸዋል፤ ይሁንና ብዙጊዜ በስቃይ ውስጥ መሆናቸውን ሲመለከቱ «አልሞተም እንዴ? ዛሬስ አልቆለታል!» እያሉ ይዘባበቱባቸው እንደነበር ዛሬ ላይ ሆነው ሲያስታውሱት እንባ ይተናነቃቸዋል። አላፊ አግዳሚውም «ቱቱቱ...! አልቆለታል!» ከማለት ውጪ ላንሳህ እንኳን ብሏቸው አለማወቁ ደግሞ እጅጉን በአገራቸው ልጆች እንዲያዝኑ እንዲሁም ከተያዘ ማንም ሰው እንደማያግዘው ያዩበት ወቅት መሆኑን ያስረዳሉ።

እንዲህ በሞት ጣር ውስጥ ሆነው ግን በፈጣሪያቸው አንድ ተስፋ ነበራቸው። እንደ እርሳቸው ወገን ዘመድ ሳይኖራቸው ጧሪና ተንከባካቢ ሳያገኙ በያሉበት የወደቁ ሰዎችን ማገዝ፤ በተሰጥኦቸውም አገራቸውን ማስጠራትንም ሁልጊዜ ይሻሉ፤ የዘወትር ጸሎታቸውም ነበር። ወገናዊ በጎ አሳቢነትም ጭምር በውስጣቸው እንዳለ ይናገራሉ። ዛሬ ደግሞ እርሳቸው ማድረግ ባይችሉም አሁን ለዚህ ያበቃቸው ሰው ይህንን ሲያደርግ ሲመለከቱ ሆኖልኛል የሚል ተስፋ ጭሮባቸዋል። ችግረኞችን  ከያሉበት በመሄድ ገላና ልብሳቸውን በማጠብ፣ ምግብ በማጉረስና ችግራቸውን ለሰው በመናገር መርዳት የሚችል ሰው በማየታቸውም ደስታቸው እጥፍ ድርብ መሆኑን ያስረዳሉ። ምክንያቱም እርሳቸው አሁንም ቢሆን ይህንን ማድረግ አይችሉማ።

ሰዎች በአግባቡ ሳያውቁና ሳይገነዘቡ በችኮላ ያልተገባ ምላሽ መስጠታቸውን ዛሬ ላይ ሲመለከቱት ተገቢ እንዳልሆነ ይገነዘባሉ። ምክንያቱም ያልተገባ ምላሽ ከሚሰጡት መካከል እርሳቸው አንዱ ስለነበሩ ነው። በድልድዩ መሀል በቀዝቃዛው መሬት ላይ ፍራሽ እንኳን ሳይኖር ማዳበሪያ አንጥፈው በሚተኙበት ወቅት እንደርሳቸው የተፈተነ አልነበረም። በተለይ ክረምት ሲሆን ወንዙ ሲያሻው በላያቸው ላይ አለያም በጎናቸው እያለፈ ተነስ ሲል ይቀሰቅሳቸዋል። በሽታውም ከመጠን በላይ ይጫወትባቸዋል። ከዚያ አልፎ በቅጡ እንኳን የሚለብሱት ነገር ስላልነበረ ብርዱም አንጀታቸው ውስጥ ዘልቆ ይገባል። ይባስ ብሎም ልብሳቸው ቶሎቶሎ ስለማይታጠብና ስለማይቀየር የተባይ አይነት ይፈራረቅባቸዋል። ኧረ ስንቱ ይነሳል፤ ብዙ ስቃይን አሳልፈዋል።

 ይሁንና ሊያነሷቸው የመጡትን ግን «ከዚህ አልሄድም፤ ድልድዩ እንደሚፈለግ ስለሰማሁ እኔን ሌላ ቦታ አውጥታችሁ እንድትጥሉ የተላካችሁ መሆናችሁን አውቃለሁ። ስለዚህም እንዳትነኩኝ አለበለዚያ እራሴን እዚሁ አጠፋለሁ» ያሏቸው ነገር መቼም እንደማይረሱት ይናገራሉ። እነርሱ ግን ችግረኞችን የመርዳት አላማን አንግበው የመጡ ስለነበሩ በትህትና መልሳቸውም ያስደንቃ ቸዋል። ባለታሪኩ እንግዳችን መንገደኛውም እሰይ እንኳን ከዚህ ተነሳ በሚል አስተያየት እየገረመሙ ይሄዳሉ እንጂ ሊያድኗቸው እንዳልወደዱም ያስታውሳሉ።  ልብስና ሌሎች አላስፈላጊ ቁሶችን በዚያው በመተው በንጹህ ብርድ ልብስ ጠቅለው መኪና ላይ ጭነውኝ እንዳመጧቸው ይገልጻሉ። ሆኖም እንዲህ ዛሬ ላይ እስከደረሱበት ጊዜ ቢንከባከቧቸውም ለጊዜው ግን ብዙም እምነት አልጣሉባቸውም ነበር፤ እንደውም «ከጊዜ ጊዜ መቼ አውጥተው ይጥሉኝ ይሆን» የሚል ስጋት አድሮባቸው እንደነበር አጫውተውኛል። ይህ ደግሞ ሰዎች በሚገባ ነገሮችን ሳያገናዝቡ በምንም መልኩ ሌሎችን ማስቀየም እንደሌለባቸው ትምህርት የሰጣቸው ጊዜ መሆኑንም ነው የነገሩኝ።

እንግዳዬ አርቲስት መኮንን እንደሚሉት፤ ካገኙዋቸው በኋላ ውሃ ከቧንቧ ሲያጡ ከወንዝ በጀሪካን እየቀዱ ቁስላቸውንና ደማቸውን ሳይጠየፉ ገላቸውንና ልብሳቸውን በማጠብ፤ ሰዎች የሚሰጧቸውን ምግብን በማጉረስ ይንከባከቧቸው ነበር። ይህ ደግሞ አሁን ላይ ከሕመማቸው ማገገም እንዲችሉ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል። ምግብና እንክብካቤም ያገኛሉ። ሰብሳቢ አግኝቼያለሁ ይመስገን!! እያሉ ደጋግመው ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉም። በእዚህ አቅመ ደካማ ሰዎች መርጃ ቤት ውስጥ ከምስረታው ጀምሮ በርካታ ዓመታትን እንዲያሳልፉ ሆነዋልም።

ዛሬ ጉልበታቸው ርዶ አቅመ ደካማ ቢሆኑም «ተንከባካቢ አግኝቼያለሁ። የሰበሰበን እኮ የእግዚአብሔር ሰው እንጂ የገንዘብ ሰው እንዳይመስልሽ! እኛን የሚያበላ ስንት ደካማን የሚያገላብጥ ነው። ቆሻሻ ልብሳችንን እያጠበና እያጎረሰ ነው የሚንከባከበን፤ ይህን ማን ያደርገዋል!?» አሉኝ በህመማቸው ውስጥ ሆነው በደከመ ድምጻቸውም የሰበሰባቸውን ማንነት ለመንገር በሚያደርጉት ጥረት። ለእኔ ቆሞ መሄድ ከፈጣሪ ቀጥሎ አስተዋጽኦ ያደረገው እርሱ ነው በማለትም አድናቆታቸውን አክለው ነግረውኛል።

የሥራ ሁኔታ

  እንግዳዬ የዛሬን አያርገውና ቀድሞ በእሳቸው ድምጸ መረዋነት የማይመሰጥ አልነበረም። ሽክ ባለው አለባበሳቸው ተውበውና ጥበብ በሚፈልቅበት መድረክ በሙዚቀኞች ታጅበው ብቅ ሲሉም የሚቀበላቸው ጭብጨባና ፉጨት ቀላል አልነበረም። የዛኔ ለተመልካቾች የሚያቀርቧቸው ጥዑመ ዜማዎች ብዙዎችን ይማርካል። ሳያስቡትም ከመቀመጫ የሚያስነሳ እንደነበረ ያስታውሳሉ። እሳቸውንና ስራዎቻቸውን የሚወዱም  በተለየ አድናቆትና  በጋለ ጭብጨባ ያጅቧቸው እንደነበር የያኔ ትዝታቸው ነበር።

በ1960ዎቹ አካባቢ በፖሊስ ኦርኬስትራ ውስጥ ከሚታወቁ ሙዚቀኞች መሀል አንዱ ነበሩ። በሚጽፏቸው ግጥምና ዜማዎች፣ በሚያንጎራጉሩትም የሱዳንኛ ዘፈኖች ብዙዎች ያውቋቸዋል። የዛኔውን የጥበብ ሰውና ሙዚቀኛ መኮንን ሽፈራውን ማለቴ ነው። ከልጅነት ዕድሜያቸው አንስቶ ያደጉበት የሙዚቃ ህይወት ቆይቶ እንጀራቸውም ነበረ። በዚህ ደግሞ የትውልድ አገራቸውን ሆሳዕናን ተሰናብተው ወደ አዲስ አበባ እንዲዘልቁ አድርጓቸዋል።

በወቅቱ ይዘውት የመጡት ማስረጃም ማንንታቸውን የሚገልጽና የተለየ ችሎታቸውን የሚያረጋግጥ ነበር። የፖሊስ ኦርኬስትራን በቅጥር ከተቀላቀሉ በኋላ እሳቸውን ከሚመስሉ ባለሙያዎች ጋር ሆነው በጥበብ ዘርፉ እንዲቀጥሉ ታዘውም ነበር ወደዚህ ቦታ እንዲያመሩ የሆኑት። እናም ከእነዚህ የጥበብ ሰዎች ጋር ሥራቸውን ቀጠሉ። በአጭር ጊዜ ያገኙት እውቅናና አድናቆት ግን በሌሎች ዘንድ በመልካም ጎን እንዳይታዩ አደረጋቸው። የበርካቶችን አድናቆት በቀላሉ ማትረፍ መቻላቸውም እንዲሁ ከእርሳቸው በፊት በጉብዝና የሚታወቁትን ሰዎች  ጥርስ አስነከሰባቸው።

አለቆቻቸው ምክንያትና ሰበብ እየፈለጉ ሲጎነትሏቸው ደግሞ እንግዳዬን በእጅጉ ከፋቸው። ቆይቶም እርሳቸውን ማሸማቀቅና ከዚህ ማስለቀቅ የሚቻለው ሙያውን በውትድርና ቅጥር እንዲቀላቀሉ ሲደረግ መሆኑን በማሰብ ጥያቄ አቀረቡላቸው። በወቅቱ ወታደር አልሆንም ማለት አይደለም በሙዚቃው ዘርፍ ለመቀጠል የመኖርና የመሞት ጥያቄን ለማስተናገድ እንኳን አያስችልም። በሞት መቀጣት ብቻ ነው አማራጩ። ነገሩ ሥራ ከመልቀቅም በላይ ነው። እናም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ከራሳቸው ጋር የሀሳብ ፍጭት ውስጥ ገቡ። በኋላም የቀረበላቸውን ጥያቄ ላለመቀበል ወሰኑ።

ብገደልም ልገደል በሚል ስሜት ተቀመጡም። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ጠቅላይ አዛዡ በሁለቱም ስርዓት ውስጥ ያለፉ ስለነበሩ አስጠሯቸውና ለመጀመሪያ ጊዜ ተደርጎ የማያውቀው ነገር በእርሳቸው ላይ እንዲፈጸም አዘዙ። እድል ፊቷን ሰጠቻቸውናም ወታደር ለምን መሆን እንዳልፈለጉ ተጠየቁ። እርሳቸውም ምክንያታቸው ምን እንደነበር በሚገባ አስረዱ። ምንም ቅጣት ሳይጣልባቸው ቦታውን ለቀው ወጡ። እሺታቸውን ገልጸው የውስጣቸው ሰላምና ምቾት ተመሰቃቅሎ ከሚወዱትና ከሚያከብሩት ሙያ ራቁ። በድንገትም የሙዚቃ ቡድኑን ተሰናብተው ወጡ።

 በሙያ ፍቅር ውስጣቸው የሚነደው መኮንን ለሙዚቃ ያላቸው አክብሮት አሁንም እንዳለ ነበርና ነገር ግን ትላንት በጎ ያልነበረው አጋጣሚ ነገ እንደማይደገም በማሰባቸውም  ሌሎች አማራጮችን መፈለግ ጀመሩ። ጥቂት ቆይቶ ብሄራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ራሳቸውን ሲያገኙትም ያለፈውን ሁሉ ረስተው በድምጻዊነት ስራቸውን ያጧጡፉት ገቡ። እዛም ግን ያሰቡት አልተሳካም። እንደፈለጉትም በመድረኩ ሳይገናኙና በአድናቂዎቻቸው አጀብ ሳይባሉ ያው የተከተላቸው የቅናት መንፈስ ከዚህም ቤት እንዲለቁ አስገደዳቸው። ተስፋ የማይቆርጡት መኮንን ግን መልሰው በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት የመቀጠር ዕድል ገጠማቸውና እዚያ ሥራቸውን ጀመሩ። ውስጣቸው የሚንቀለቀለው የጥበብ ፍቅር አሁን ማረፊያ እንደሚያገኝ ገምተዋል።

 በየጊዜው ያዳበሩት ልምድና ያተረፉት እውቅናም የአድናቂዎቻቸውን ቁጥር አበራክቶታልም። ይሁን እንጂ እዚህም ቢሆን  የነበረው አቀባበል ተመሳሳይ ሆነ። የወቅቱ ወታደራዊ መንግስት ፍላጎትና የእሳቸው የሙያ ትኩሳት በአንድ አልተጓዙም። ስለዚህም አሁንም ወጣቱ ሙዚቀኛ ስራውን ከመልቀቅ ሌላ ምርጫ አልነበረውም። ቆይቶ በድምጻዊ ታምራት ሞላ ጠቋሚነት በምድር ጦር ኦርኬስትራ ለመቀጠር  ያገኙት ዕድልም  ሳይሳካ ቀረ። ከዚህ በኋላ ድምጻዊ መኮንንና የሚወዱት ሙያ እስከወዲያኛው ተለያዩ። በሌላ ሙያ መቀጠልም አስጠላቸው።

ስለዚህም የትላንቱ ታዋቂ ሰው ራሳቸውን ለማኖር ሲሉ ሲያገኙ በጉልበት፣ አንዳንዴም በዘበኝነት እየተቀጠሩ ህይወታቸውን መግፋት ቀጠሉ። አልፎ አልፎ በግል ትምህርት ቤት የሚያገኟቸውን ተማሪዎች ማስጠናትንም ኑሯቸውን ለመደጎም ሲጠቀሙበት ቆይተዋል። በዚህ ሁኔታም ዓመታትን አሳለፉ። ያው እያደር ጤንነታቸው ሲጓደል ወደቁ እንጂ። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የጉልበት ሥራ ላይ በስፋት መሳተፋቸው ነበር። ባሳለፉት ዘመን በቂ ጥሪትና የተሳካ ትዳር፣ የኔ የሚሏቸው ልጆችና መጠጊያ ታዛን የላቸውም። ላባቸውን አንጠፍጥፈው ቤታቸው ሲገቡ ጉዳታቸውን የሚያክምላቸውና የሚንከባከባቸውም ሰውም የለም። ስለዚህም የሰውነታቸው መድከምን ተከትሎ የዲስክ መንሸራተቱ መጣ፤ ከወገባቸው በታች ሰውነታቸው ከዳቸው።

ይሄኔ ነበር እንግዳዬ ድምጻዊ መኮንን የሰዎች እጅ መናፈቅ የጀመሩት። ይጠሩት ዘመድ፣ ይጠጉበት ቤት አልነበራቸውም፤ ሳይከፍል ማኖር ደግሞ ከባድ እንደሆነ ማንም ይረዳል። እናም ተስፋ መቁረጥ፣ ህመምና ድህነቱ  ሲያንገላታቸው ከአንዱ የጎዳና ጥግ ወደቁ። ደግመው አልተነሱም። የክረምቱ ዝናብ፣ የበጋው ጸሀይና ሙቀትም ለዓመታት ተፈራረቀባቸው። ማንነታቸውን የሚያውቁ ለዕለት ጉርሳቸው አልነፈጓቸውም። ከሳንቲሙ፣ ከእንጀራና ከዳቦው ሲያካፍሏቸው ቆዩ።

በየቀኑ በዛ መንገድ የሚመላለሱ ጥቂት ሰዎች እይታ ግን ከሌሎች የተለየ ነበር። ብዙዎች እጃቸውን  ለሚዘረጉላቸው ሰው የነበራቸው ትኩረት ከሀዘኔታ የዘለለ ሆነና አንድ ቀን የመኮንን የላስቲክ ጎጆ ሲቃኟቸው በነበሩ ሰዎች እጅ ድንገት ተገለጠ። ያው ከላይ እንደተቀመጠው ሆነና ዛሬ ላሉበት ህይወት በቁ።

ተሰጦ መቼም እንደማይከዳና እንደማይጠፋ የተረዳሁትም ከእርሳቸው ነው። ምክንያቱም «እስኪ ዛሬና በፊት የነበረዎት የድምጽ አወራረድ ምን ያህል ልዩነቱ ይጎላል» ብዬ አንድ የሱዳንኛና የአማርኛ ዘፈን እንዲጫወቱ ጠየኩዋቸው። እርሳቸውም ያለምንም ማመንታት ፈቃደኝነታቸ ውን ገልጸው በሚያስረቀርቅ ድምጻቸው የሚወዱትን መስፍን ኃይሌን «መንገዱ ረዘመ» በሚል አንጎራጎሩልኝ። ከዚያም ሱዳንኛውን ቀጠሉ። ያው እኔም ብዙ ስለማይገባኝ አቋረጥኳ ቸውና ድምጻቸው እንዴት እንደሆነ ጠየኳቸው።« ከድካሙ ጋር ተያይዞ ልዩነቶች አሉት። ነገር ግን አልጠፋም። ምክንያቱም ተሰጥኦን ሊያጠፋ የሚችለው ሞት ብቻ ነው» አሉኝም።

እንግዳዬ ሲያንጎራጉሩ ዛሬ ላይ ድምጻቸው እንዲህ ከሆነ በፊት ምን እንደሚመስል ለመናገር ከበደኝ፤ ወደኋላ ተመልሼም እየተመለከትሁ  ስንቶች በእርሳቸው ድምጽ አወራረድ እንደ ተማረኩ በማሰብ ምነው የዛን ጊዜ በነበርኩ አሰኘኝ። በጣም ደስ የሚልና የሚያማልል ድምጽ አላቸው። እርሳቸው ባሉኝ ደረጃ ደግሞ ምን እንደሚመስል መገመት እንኳን ይከብዳል። ይሁንና ስለእርሳቸው የህይወት ተሞክሮ ብዙ ማውራትና መናገር ይቻል ነበር ግን ጊዜና ቦታ ገድቦኛል። ይሁን እንጂ ከዚያ በፊት እርሳቸው ያሉኝን ነገር ላስቀድም።

«ጥሩ ማድረግ ጥሩ ነው። ሁልጊዜ ጥሩ ነገር አድርጊ። ፈጣሪ ከችግር ሁሉ ይጠብቅሽ፤ ምክንያቱም ችግር ሲገጥምሽ የሚሸሽ ብዙ ነው፤ ካለሽ ደግሞ በዙሪያሽ የሚከብሽ ይበረክታል። እናም ባለሽና ጉልበትሽ ሳይደክም ችግረኞችን ለማየት ሞክሪ» ብለው ትዕዛዝ መሰል መልዕክታቸውንና ምርቃታቸውን ሰጡኝ። በልቤ ምርቃቱን ተቀብዬ በተራዬ ጤናቸው እንዲለመስ ተመኝቼ ልነሳ ስል እጄን ያዝ አድርገው በአሁኑ ወቅት ደስተኛ እንደሆኑ፣ ሰው ለይተው ማወቅና ችግራቸውን መናገር መጀመራቸውንና ወደፊት ፈጣሪ ከፈቀደ ድነው ያሰቡትን እንደሚያደርጉም ነገሩኝ። እኔም ተሰናብቼ ወጣሁ። የእኔም መዝጊያ ይኸው ነው፤ በማንኛውም ጊዜ ደግነትን ገንዘብ እናድርግ የሚለው። ሰላም!!

ጽጌረዳ ጫንያለው

Published in ማህበራዊ

የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከታህሳስ 3 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለ17 ቀናት ያካሄደው  የሁኔታዎች ግምገማ ውሳኔዎችንና ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል፡፡ የመግለጫውን ሙሉ ቃል እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

የድርጅታችን የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከታህሳስ 3 ቀን ጀምሮ ላለፉት 17 ቀናት አገራችን የምትገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ መነሻ በማድረግ ሰፊና ዝርዝር የሁኔታዎች ግምገማ አካሂዷል፡፡ ስራአስፈፃሚ ኮሚቴው በዚህ ስብሰባ ቀደም ሲል የተጀመረው የመታደስ ሂደትና የደረሰበትን ደረጃ እንዲሁም በአገራችን የሚታዩ የቆዩና ወቅታዊ ችግሮችን ከነዝርዝር መገለጫቸው በመለየት በመንስኤና መፍትሄዎቻቸው ላይ መክሮ የሃሳብ አንድነትና መተማመን ፈጥሯል፡፡ ችግሮቹን በመቅረፍ በእስካሁን ትግላችን የተመዘገቡ መልካም ውጤቶችን አስጠብቆ ለማስቀጠል የሚያስችል ቁርጠኝነትና ጠንካራ መግባባትን አረጋግጦ ወጥቷል፡፡

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች

ድርጅታችን ኢህአዴግ አገራችንን በለውጥ ጎዳና መምራት ከጀመረበት ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም የህይወት መስኮች መሠረታዊና ተስፋ ሰጭ ለውጥ ሲመዘገብ የቆየ ቢሆንም፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለውጡን በተጀመረው ስፋትና ግለት ለማስቀጠል የሚደረገውን ጥረት የሚፈታተኑ ችግሮች እየታዩ መምጣታቸውን ይገነዘባል፡፡ አገራችን በአንድ በኩል በተከተልነው መሠረታዊና ትክክለኛ አቅጣጫ በተገኙ መልካም ውጤቶች እጅግ የሚያስጎመዥ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በፈፀምናቸው ስህተቶችና ከዕድገታችን ጋር ተያይዘው በተከሰቱ አዳዲስ ለውጦችና ፍላጎቶች ምክንያት ለጊዜውም ቢሆን በአሳሳቢ ወቅታዊ ችግሮች ተወጥራ የቆየችበት ሁኔታ መፈጠሩን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በትኩረት ገምግሟል፡፡

ለሁሉም የአገራችን ህዝቦች ግልፅ እንደሚሆነው ለበርካታ ዘመናት በማሽቆልቆል ሂደት ውስጥ ለማለፍ የተገደደችው አገራችን ለ25 ዓመታት ቀና ብላ ስትጓዝ ቆይታለች፡፡ ይህም በሁሉም አገር ወዳድ ዜጎች የሚታመንበትና ዓለምም የመሰከረለት ነው፡፡ የኢኮኖሚ ውድቀትና ማሽቆልቆል ተገትቶ ለሩብ ምዕተ ዓመት የዘለቀው አገራዊ ዕድገት ኢትዮጵያችን በትንሳኤ ጎዳና መገኘቷን አብስሯል፡፡ ህገመንግስታዊ ዴሞክራሲያችን የግልና የቡድን መብቶችን በማስከበር የሰላምና የእድገት መሰረት እንደሆነ በእነዚሁ ዓመታት ተረጋግጧል፡፡ ብዝሃነት የኢትዮጵያችን መሰረትና መገለጫ እንደሆነ በመቀበል ይህንኑ በአግባቡ ለማስተዳደር ያደረግነው ጥረት አገራችን ዜጎች ለረጅም ዓመታት በፍቅርና መከባበር የሚኖሩባት የሰላም አገር እንደሆነች አስመስክሯል፡፡ ይሁንና ይህ የሚያስጎመዥ እውነታ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመታየት ላይ ባሉ ጊዜያዊ ችግሮች የተነሳ ለአደጋ እየተጋለጠና ለሁሉም ማህበረሰቦቻችን የስጋት ምንጭ መሆን በጀመረ አዲስ ክስተት መልክ የሚገለፅበት አዝማሚያ ሰፋ ብሎ ታይቷል፡፡ ከዚህ የተነሳም መላ የአገራችን ህዝቦች ኢትዮጵያችንን ከገጠሟት ጊዜያዊ ችግሮች በማውጣት በትግላችን የተመዘገቡ ስኬቶችን ለመጠበቅና ለማስፋት፤ ድክመቶችንና አደጋዎችን ደግሞ በቁርጠኝነት ለማስተካከል የሚሹበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ መንግሥትና የለውጡን ሂደት የሚመራው ድርጅታችንም ለዚህ የህዝብ ጥያቄ አስተማማኝ ምላሽ የሚሰጡበት ሁኔታ እንዲፈጠር አጥብቀው ሲጠይቁ ቆይተዋል፡፡

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከሁለት ሳምንት በላይ ጊዜ ያካሄደው ግምገማ በዚህ የህዝባችን ልባዊ ፍላጎትና ቅን አገራዊ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተና ለዚሁም መላው ድርጅታዊ አቅሙን ተገዥ ለማድረግ በሚያስችል ቁርጠኝነት የተካሄደ ነው፡፡ በመሆኑም ስብሰባው በትናንትናው እለት በመላው የአገራችን ህዝቦች ከባድ ተጋድሎ የተመዘገቡ ስኬቶችን ለመጠበቅና ለማስፋት እንዲሁም ከምንም ነገር በላይ በአመራር ድክመት የተፈጠሩትን አደጋዎችና ስጋቶች ለመቅረፍ በሚያስችል ስምምነትና መግባባት ተጠናቋል፡፡

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለፉት አስራ ሰባት ቀናት ባደረገው ግምገማ በየደረጃው ባሉ የአመራር እርከኖች በተለይ ደግሞ በከፍተኛው አመራር ደረጃ የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ እጦት ስር እየሰደደ እንደመጣ አረጋግጧል፡፡ ይህም ሐሳብ በነፃነት የሚንሸራሸርባቸውን የመታገያ መድረኮች የሚገድብና የሚያጠብ ስለዚም ደግሞ በአመራሩ ውስጥ የአመለካከትና የተግባር አንድነትና ጥራት እንዳይፈጠር መሰናክል ሆኖ እንደቆየ ተመልክቷል፡፡ ይህ ችግር በዋነኛነት በድርጅታችን ከፍተኛ አመራር ደረጃ ከታየው የተዛባ የስልጣን አተያይና አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የተከሰተ ሲሆን ችግሩ የድርጅታችን አይነተኛ መለያ የሆነውን ዴሞክራሲያዊነት በማዳካም ሳይወሰን ስልጣን የህዝብ መገልገያ እንዲሆን የጀመርነውን መልካም ጉዞ ለአደጋ ያጋለጠ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ዴሞክራሲ እየጠበበ አድርባይነት በመስፋፋቱ ምክንያት በግልጽነትና በመርህ ላይ ተመስርቶ ከመተጋገል ይልቅ መርህ አልባ ግንኙነትና አካሄድ ማስፈን የተለመደ ስልት ወደመሆን ተሸጋግሯል፡፡ ይህን የመሰለው በጠባብ ቡድናዊ ጥቅሞች ላይ የተመሰረተ መርህ አልባ ግንኙነት ኢህአዴግና አባል ድርጅቶቹን የማዳከም ውጤት አስከትሏል፡፡ ልማታዊ መንግሥታት በጠንካራ ዲስፒሊንና የሃሳብና የተግባር አንድነት የሚታወቁ ሆኖ እያለ ተገቢ ባልሆኑ ጥቅሞች ላይ የተመሰረቱት የቡድን ትስስሮች ልማታዊ መንግሥታችንና ድርጅታችን ተልእኮአቸውን በብቃት እንዳይፈፅሙ ከፍተኛ መሰናክል ሆኖ እንደቆየ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው አረጋግጧል፡፡

በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴያችን ግምገማ መሰረት ማንኛውም መርህ አልባ ቡድናዊ ትስስር ከምንም ነገር በፊትና በላይ እያንዳንዱን ብሄራዊ ድርጅትና በእሱም የሚመራውን ህዝብ የሚጎዳ አደገኛ ጉዳይ ነው፡፡ በመቀጠልም በግንባራችን የሚመራውን የጋራ ትግልና አገራዊ የለውጥ ሂደቱን ለአደጋ የሚያገልጥ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ስራአስፈፃሚ ኮሚቴው በየትኛውም ክልል ሆነ ብሄራዊ ድርጅት የሚከሰቱ መርህ አልባ ጉድኝቶች በጥልቅ እየተፈተሹ ሊወገዱ እንደሚገባ ወስኗል፡፡

እንደሚታወቀው በአገራችን የሚገነባው ፌዴራላዊ ስርዓት መላ የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦች ለዘመናት ያካሄዱት ትግል ውጤት ነው፡፡ አዲሲቱ ኢትዮጵያ ከየትኛውም ህብረብሄራዊ አገር የምትለየው በዝሃነትን በማወቅና በማክበር ነው፡፡ ለ25 ዓመታት የተገነባው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የቋንቋ፣ የባህል፣ የታሪክ እኩልነተን አረጋግጧል፡፡ የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው ካልሆነ በቀር በሌላ የማይተዳደሩበት ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በፌዴራላዊ አስተዳደራዊ ስርዓታችን በእኩልነትና በመተሳሰብ የሚሳተፉበትን ሁኔታም አመቻችቷል፡፡ በዚህ የተነሳ ስርዓቱ ለበላይነትና የበታችነት የማይመች ሆኖ ተዋቅሯል፡፡ በተግባርም እኩልነት እንጂ የባላይነትም ሆነ የበታችነት የማይፈጠርበት ስርዓት ተገንብቷል፡፡ ይህንን መሠረታዊ መርሆ የሚነካ ማንኛውም ዝንባሌ የበላይነትን በዘላቂነት ሊፈጥር የማይችልና ከመናቆር ውጭ ሌላ ውጤት የማያስገኝ እንደሚሆንም ይታመናል፡፡ ከዚህ በመነሳት ለሩብ ምዕተ ዓመት በእኩልነትና በሰላም የዘለቀው ስርዓታችን የዚህ ውጤት እንደሆነ ሥራ አስፈፃሚያችን በድጋሚ አረጋግጧል፡፡ በመሆኑም በማንኛውም ሽፋን ይህንን የእኩልነት ስርዓት ለማዳከም የሚደረግ ሙከራ ተቀባይነት እንደሌለውና ሊመከት እንደሚገባው ወስኗል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በአንድ ወይም በሌላ ብሔር ህዝብና ድርጅት ስም እየማሉና እየተገዘቱ ጥገኛ ፍላጎታቸውን ለማርካት የሚንቀሳቀሱ ወገኖችን እንቅስቃሴ ማክሰም እንደሚገባ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ሁሉም ብሔራዊ ድርጅቶች በሚያስተዳድሩት ክልል ውስጥ ያሉ ጥገኞችን ያለልዩነትና ማመንታት  መታገል እንዳለባቸው ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ሥራ አስፈፃሚው በድርጅታችን የዴሞክራሲ መጥበብ እዛው በዛው የውሳኔዎችን በታማኝነትና በቁርጠኝነት የመፈፀም ዲሲፒሊንን እያላላ እንደመጣ አረጋግጧል፡፡ በዚህ የተነሳ በድርጅትና በመንግሥት ቋሚ መመሪያዎች በመገዛት መፈፀም የነበረባቸው ተግባራትና መሰጠት የነበረባቸው የዕለት ተዕለት ውሳኔዎች እየቀሩ በብዙ የመንግሥት መ/ቤቶች ህዝብ የሚጠብቃቸው አገልግሎቶች የማይሟሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

በአጠቃላይ በድርጅታችን በተለይም ደግሞ በሥራ አስፈፃሚው ውስጥ የታየው የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ ችግር አደጋው በድርጅቱ ውስጥ ብቻ ታጥሮ የቀረ አልነበረም፡፡ የሕዝብ መብትን በማክበርና ተገቢውን ህጋዊ አገልግሎት የመስጠት ግዴታን ባለመወጣት ጭምር የሚገለፅ ነበር፡፡ ከዚያም አልፎ ዴሞክራሲያችንን ማስፋትና ማጠናከር ሲገባ በተለያዩ መንገዶች የማጥበብ አዝማሚያም ተስተውሏል፡፡ ህገ መንግሥታዊ ስርዓታችን ልዩ ልዩ ጥቅሞችና ፍላጎቶች እንዲሁም በእነዚህ ላይ የተመሰረቱ ልዩነቶች በዴሞክራሲያዊ፣ ህጋዊና ሰላማዊ መንገድ እንዲስተናገዱ በቂና አስተማማኝ እድል ከፍቶ እያለ አመራራችን ዴሞክራሲውን የማስፋት ግዴታውን ባለመወጣቱ ችግሮችና ልዩነቶች በግጭት መንገድ የሚፈቱበት ሁኔታ እንዲፈጠር አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ይህም ለሠላማችን  መታወክ የበኩሉን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡

ለመላው የአገራችን ህዝቦች ግልፅ እንደሚሆነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርከት ባሉ የአገራችን አካባቢዎች ሰላምና መረጋጋት እየደፈረሰ ሁከት የዕለት ተዕለት ክስተት እየሆነ መጥቷል፡፡ በክልሎችም ሆነ በክልሎች መካከል በልዩ ልዩ ሰበቦች የሚከሰተው የሠላም መደፍረስ ለዜጎቻችን አሳዛኝ ሞት መበራከትና መቁሰል እንዲሁም ከባድ መፈናቀል ምክንያት ሆኗል፡፡ በተጨማሪም ከፍተኛ የንብረት ውድመትና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መገታት አስከትሏል፡፡ ይህ ለረጅም ዓመታት በሰላም በኖረችው አገር ውስጥ የስጋት መንፈስና ጭንቀት ፈጥሯል፡፡  ከየቦታው እየተነሱ ያሉ ግጭቶች ከሰው ሞትና ከንብረት ውድመት በዘለለ የሃገራዊ ሕልውናችን ለአደጋና ሕዝባችንን ለጥፋት ቋፍ ያደረሱበት ሁኔታ ከመኖሩ በላይ ለውጭ ጥቃት ተጋላጭነታችንን የመጨመር ውጤት አስከትለዋል፡፡ ይህም በአጭር ቃል የመበልፀግ ተስፋና የሐገራዊ ሠላም መናጋት የተፋጠጡበት ሁኔታ ላይ እንድንገኝ አድርጎናል፡፡ ከዚህ በመነሳት ስራአስፈፃሚ ኮሚቴያችን ህገመንግስታዊ ዴሞክራሲያችንን በታማኝነት ተግባራዊ ማድረግ ብቻ ሳይሆን መድረኩ የሚጠይቀውን ሁኔታ መነሻ በማድረግም ማስፋትና የግጭት መንስኤዎችን መቅረፍና የአገራችንን ሠላም ወደተለመደው አስተማማኝ ሁኔታ በአጭር ጊዜ መመለስ እንደሚገባ ወስኗል፡፡

በአገራችን የሚገነባው ህገመንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በፍላጎትና ጥቅሞች ብዝሃነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በድርጅታችንና በመንግሥት መሪነት ለ25 ዓመታት የቀጠለ ቢሆንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአስተሳሰብ ብዝሃነት በአግባቡ እንዲገለፅ የሚያደርግ ተጨባጭ ሁኔታ እየተዳከመ መጥቷል፡፡ ይህንን ችግር በጊዜና በአግባቡ ተገንዝቦ ማስተካከል የሚገባው ድርጅታችን ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ረገድ ያሳየው ዳተኝነት የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱን ችግር እንዲገጥመው አድርጓል፡፡ የዴሞክራሲ ምህዳሩን የማስፋት ጉዳይ ምንም እንኳ በአዋጅና በድርጅታችን በጎ ፈቃድ ላይ ብቻ የሚመሰረት ባይሆንም በዚህ ረገድ ልንወስደው ይገባን የነበረውን እርምጃ ከመውሰድ አንፃር ሰፊ ክፍተት እንደነበር ሥራ አስፈፃሚው ይገነዘባል፡፡

ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሁነኛ ድርሻ ካላቸው ተቋማት መካከል የሃገራችን ሚዲያና ፕሬስ በሚገባው ደረጃ ነፃነታቸው ተጠብቆ የህዝብ ዓይንና ጆሮ ሆነው ያገለግሉ ዘንድ የተደረገው እንቅስቃሴ የሚፈለገውን ውጤት እንዳላመጣ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በግምገማው ተመልክቷል፡፡ በዚህ ረገድ የታየው ዘገምተኛ ዕድገት እንደተጠበቀ ሆኖ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በክልልም ይሁን በፌዴራል ያሉ የህዝብ የሚዲያ አውታሮች ሕግና ሥርዓትን ጠብቀው የማይሠሩበት ሁኔታ እያመዘነ የህዝቡን ሰላምና አብሮ የመኖር ገንቢ ባህል የሚሸረሽሩ ሰበካዎች የሚሰጥባቸው፣ ብሎም ህዝብን ከህዝብ ጋር የሚያጋጩ አጥፊ ቅስቀሳዎች የሚካሄድባቸው እየሆኑ ለመምጣታቸው የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚም ሆነ የሚመራው መንግሥት ድክመት አስተዋፅኦ እንዳደረገ ይቀበላል፡፡

አመራሩ ዴሞክራሲያዊ ህብረተሰብ በመገንባትና  በህገመንግስታዊ ስርዓታችን ዙሪያ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር እየተገባው የህዝብ የተደራጀ ሲቪል እንቅስቃሴ እንዳልተጠናከረ አረጋግጧል፡፡ በአገራችን ህገመንግስታዊ ዴሞክራሲ ዋስትና የሚኖረው ከአዋጅ አልፎ ህዝብ በተደራጀና ንቁ አኳኋን ሲሳተፍና ሲጠቀምበት ቢሆንም በዚህ ረገድ የተደረገው እንቅስቃሴ የሲቪል ማህበረሰቡን ተሳትፎ መሆን በሚገባው ደረጃ ከፍ ለማድረግ ያስቻለ እንዳልሆነ ተመልክቷል፡፡ በዚህ መሰረት በአገራችን የሚገነባው ዴሞከራሲያዊ ስርዓት የሚታይበትን የሲቪል ማህበረብ ተሳትፎና ሁለገብ እንቅስቃሴ ገደብ ከጣሉበት ችግሮች በማላቀቅ ማጠናከር እንደሚገባ ታምኖበታል፡፡ አመራሩ የዴሞክራቲክ ተቋማት ግንባታና የህዝብ የተደራጀ ተሳትፎ የሞት የሽረት ጉዳይ እንደሆነ ተገንዘቦ ባለመንቀሳቀሱ የተፈጠረውን መሠረታዊ ጉድለት ለመፍታት ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

ልክ እንደዴሞክራሲው ሁሉ በአገራችን የህልውና ጥያቄ የሆነውን መልካም አስተዳደርን የማስፈን እንቅስቃሴያችን በአመራር ድክመት ምክንያት ለበርካታ ችግሮች እንደተጋለጠ ሥራ አስፈፃሚ ኮማቴው አረጋግጧል፡፡ በዚህ ረገድ የህዝቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማስፋት፣ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ የግልፅነትና የተጠያቂነት አሰራርን ለማንገስና ውጤታማና ቀልጣፋ አስተዳደር ለመገንባት የተደረጉ ጥረቶች ያስገኙትን መልካም ፍሬ መጠበቅና ማስፋት አዳጋች ሆኖ ቆይቷል፡፡ በየደረጃው ያሉ  የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት በቅን ልቦናና መንግሥታዊ መመሪያዎችን በተከተለ አኳኋን ህዝቡን የሚያገለግሉና ተሳትፎና ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጡበት ዕድል ቀንሷል፡፡ በዚህ የተነሳ ከፍተኛ የሕዝብ ምሬት ተፈጥሯል፡፡ ሥራ አስፈፃሚው ይህ ችግር ከምንም ነገር በላይ በከፍተኛው አመራር ደረጃ በሚታይ ጉድለት ምክንያት የተፈጠረና የተባባሰ እንደሆነ አረጋግጧል፡፡ የህግ የበላይነት የማስፈን ድክመት በመታየቱ በሙስናም ሆነ በሌሎች ጥፋቶች ውስጥ የተዘፈቁ ግለሰቦችን በወቅቱ ህጋዊና አስተማሪ በሆነ መንገድ መጠየቅ ሳይቻል ቆይቷል፡፡ ዜጎች በህገመንግስቱ ዋስትና ያገኙ መብቶቻቸው የሚጥሱ ሰዎችን በህግ ተጠያቂ ማድረግ መሆን በሚገባው ደረጃ ሳይፈፀም ቆይቷል፡፡ በተጨማሪም መንግሥት የህዝብና የአገር ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በነደፋቸው ፕሮጀክቶች ዙሪያ የሚታዩ የአፈፃፀምና የስነምግባር ችግሮችን አስተማማኝና ውጤታማ በሆነ መንገድ የማረምና የማስተካከል ጉድለት ታይቷል፡፡ በዚህ የተነሳ አገራችንን በሁሉም መስክ ተወዳዳሪ ሊያደርጉ የህዝባችንን ተጠቃሚነት ሊያሰፉ የሚችሉ ፕሮጀክቶች፣ የጊዜ የዋጋ ንረትና የሃብት ብክነት የሚታይባቸው ሆነዋል፡፡ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው እነዚህ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ህዝብና አገርን ያልተገባ ዋጋ የሚያስከፍሉ እንደሆኑ በመገንዘብ በአፋጣኝ እንደተስተካከሉ ማድረግ እንደሚገባ አምኖበታል፡፡ በዚህ ረገድ ይህንን የመልካም አስተዳደር ችግር በተግባር ማቃለል ሲገባ ባጉል ተስፋና በባዶ ቃልኪዳን የመሸንገል ህዝበኛ አዝማሚያዎች በጥብቅ መመከት እንዳለባቸው ወስኗል፡፡

ድርጅታችን የሁሉም ህዝቦች እኩልነት በተከበረባት አገራችን አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባትን መርህ ተከትሎ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ በተጨባጭም አገራችንን ከመበታተን ቋፍ አውጥቶ አዲስ ዓይነት ዴሞክራሲያዊ አንድነትና የእኩልነት ትስስር በመገንባት ረጅም ርቀት ተጉዟል፡፡ ይህ በአገር አቋራጭ የመሠረተ ልማት አውታሮች የማይበጠስ ትስስር እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በሃገራችን በየደረጃው እየተካሄዱ ያሉና ሊካሄዱም የሚገባቸው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶች የድርጅታችን ሃገራዊ ራዕይና የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችንን በሚያጠናክር መልክ በማስኬድ ረገድ ቁጥራቸው የማይናቅ ጉድለቶች በአመራሩ ተፈጽመዋል፡፡ በአጭሩ በሕብረተሰባችን ዘንድ ህገመንግሥታዊ ሥርዓቱን፣ ልማታዊ አስተሳሰብና፣ በብዝሃነት ላይ የተመሠረተ ኢትዮጵያዊ አንድነት በማጠናከር ረገድ የተሰራው ሥራ መሆን የሚችለውን ያህል ውጤት ሳያመጣ እንደቀረ ሥራ አስፈፃሚው ባደረገው ግምገማ ማረጋገጥ ችሏል፡፡ በዚህ የተነሳ ብሄረሰባዊና አገራዊ ማንነትን አስተሳስሮ በመገንባት በኩል የታየውን ጉድለት በአፋጣኝና በአስተማማኝ መንገድ መፍታት እንደሚኖርብን ታምኖበታል፡፡

ከላይ የተገለፁት ችግሮችና በተራዘመ ትግል የተገነባችውን አገር ለአደጋ ማጋለጥ የጀመሩት ጉድለቶች በዋነኛነት የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር በተለይም የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ድክመቶች ናቸው፡፡ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላቱና የድርጅትና የመንግሥት ከፍተኛ ሃላፊዎች በተናጠልና በጋራ፣ ስትራቴጂያዊና ታክቲካዊ አመራር የመስጠት ሃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው የተፈጠረ ችግር ነው፡፡   በዚህ ግምገማ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴና የመንግሥት የበላይ አመራሮች ወቅቱ የሚጠይቀውን ስትራቴጂያዊ አመራር  የመስጠት ጉድለታቸው ሰፊ እንደሆነ ታይቷል፡፡ ከፍተኛ  አመራሩ ችግር አስቀድሞ የመለየት፣ ተንትኖ የማወቅ፣ የመፍቻ መንገዶች የመተለምና በዚሁ መሠረት የመፍታት ብቃቱ ወቅቱና መድረኩ ከሚጠይቀው ደረጃ ጋር አብሮ ባለማደጉ የተወሳሰበውን አገራዊ መድረክ በብቃት የመምራት ጉድለት እንደነበረበት የጋራ አቋም ተይዟል፡፡ በመሆኑም  ለተፈፀመው ስህተትና ለደረሰው ጉዳት ከፍተኛ አመራሩ ሃላፊነቱን እንደሚወስድ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ከዚህ በመነሳት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው መላ የአገራችን ህዝቦች በከባድ ተጋድሏቸው ያስመዘገቡዋቸውን ድሎች ጠብቆና አስፍቶ ለማስቀጠል ባለመቻሉ፤ እንዲሁም በድርጅታችን ውስጥም ሆነ በአገራችን ውስጥ የሚታዩ ልዩ ልዩ ችግሮችን በጊዜና በከፍተኛ የሃላፊነት መንፈስ ለመፍታት ባለመቻሉ ለደረሰው ጉዳት ሙሉ ሃላፊነቱን ከመውሰድ በተጨማሪ ለመላ የአገራችን ህዝቦችና የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎችን ልባዊ ይቅርታ ይጠይቃል፡፡ ድርጅታችን ኢህአዴግ የትግልና የለውጥ ድርጅት ብቻ ሳይሆን ለዘመናት በማሽቆልቆል ውስጥ የቆየችውን አገር ለሩብ ምዕተ ዓመት በእድገትና የለውጥ ጎዳና እንድትገሰግስ ያደረገውን ጥረትና የተመዘገቡትን ህዝባዊ ድሎች ለአደጋ የሚያጋልጥ ሁኔታ እንዲፈጠር በማድረጉም የተሰማውን ከልብ የመነጨ ፀፀት ይገልፃል፡፡ ይህ ሁኔታ እንዳይደገምም እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ በቁርጠኝትና በፅናት እንደሚንቀሳቀስ ቃል ኪዳኑን ያድሳል፡፡ ለማናቸውም ፈተና ሳይንበረከክ ከድል ላይ ድል በማስመዝገብ የመጓዝ እንቁ ታሪክ ያለው ድርጅታችን ኢህአዴግ አሁን በአገራችን የሚታየውን ሁኔታ እንደሚያስተካክልና የድል ጉዞውን እንደሚያስቀጥልም ቃል ይገባል፡፡

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከላይ በተገለፀው ግምገማና መግባባት ላይ በመመስረት ከዚህ የሚከተሉትን አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ አጣዳፊ ችግሮችን እየፈታ ለዘላቂ ለውጥ መስራት እንዳለበት ወስኗል፡፡

  1. ባለፉት 17 ቀናት ባካሄደው ግምገማ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የሕዝባችንን የዴሞክራሲና የልማት እንቅስቃሴ በማጎልበት ተሳትፎና ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥና ለማስፋት፤ አስተማማኝ ሠላም ባጠረ ጊዜ ማረጋገጥና ሕዝባችን ወደተረጋጋ ኑሮው እንዲመለስ ማድረግ እንደሚገባ በአጽንኦት ወስኗል፡፡ በዚህም መሠረት የሕዝባችንን ሰላማዊ ኑሮ የሚያውኩ ማንኛውም እንቅስቃሴዎች ከሕዝብ ጋር በመሆን በቁጥጥር ስር ለማዋል መንግሥት ሙሉ ሃላፊነት ወስዶ እንዲያስፈፅም ተወስኗል፡፡ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ላፍታም ቢሆን ጥያቄ ውስጥ ሊገባ እንደማይገባውና በዚህ ረገድ የሚታዩ የህግ ጥሰቶችን በመቆጣጠር ህግና ሰላምን በአስተማማኝ ደረጃ ማስፈን እንዳለበት ተወስኗል፡፡ በየአካባቢው በሕገወጥ መንገድ የሚደረጉ መንገድ የመዝጋት፣ የዜጎችን በነፃ የመንቀሳቀስ መብት የማወክ እንዲሁም የሕዝቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚያስተጓጉሉ የቡድንም የተናጠልም እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ይደረጋል፡፡ በወሰንም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች የሚያጋጥመውን ሞትና መፈናቀል ሙሉ በሙሉ ለማስቆም ወስኗል፡፡ በቅርቡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል መካከል ባሉ አዋሳኝ አካባቢዎች ባጋጠሙ ግጭቶች ሳቢያ የተፈጠረው የዜጎች ሞትና እንግልት እንዲሁም የመቶ ሺዎች መፈናቀል በአስቸኳይ ተገቶ ተፈናቃዮች መደበኛ ህይወታቸውን በተረጋጋ መንገድ የሚመሩበት ሁኔታ ባስቸኳይ ለማመቻቸት ወስኗል፡፡ በተጨማሪም በእነዚህ አካባቢዎች ለግጭት መንስኤ የሆኑ የሕገ ወጥ ንግድ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ፤ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴያቸው ለአደጋ እንዳይጋለጥ አስፈላጊው ጥበቃና ድጋፍ እንዲደረግ ወስኗል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የአገራችን የመከላከያ ሰራዊትና የፀጥታ አካላት በአስቸጋሪ ሁኔታ ሠላማችንን ለማስከበር ለከፈሉት መስዋዕትነት የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያለውን አክብሮት ይገልፃል፡፡
  2. ከውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ አኳያ አሁን የተጀመረውን ግምገማ መሠረት በማድረግና የትራንስፎርሜሽን አጀንዳችንን በውጤት ለማስፈፀም እያንዳንዱ ብሔራዊ ድርጅት በከፍተኛ አመራር ደረጃ የሚታይበትን ድክመት በጥልቀት ገምግሞ በግልጽነትና በተጠያቂነት ላይ የተመሠረተ የማስተካከያና የእርምት እርምጃ እንዲወስድ ወስኗል፡፡
  3. ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን እኩልነትንና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችን የመለሰ ቢሆንም ከአፈፃፀም ድክመት ጋር በተያያዘ ከቦታ ቦታ የሚታዩ የልማት አቅርቦት ልዩነቶች እንዳሉ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡ በድህነት ላይ ያስመዘገብናቸው ድሎች እንደተጠበቁ ሆነው አሁንም ቢሆን ወደ ሩብ የሚጠጋው ሕዝባችን ከድህነት ወለል በታች መገኘቱ መሆኑ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት በዚህ ረገድ ትግላችን ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው በአጽንኦት ተገልጿል፡፡ የፌዴራል የልማት ፕሮጀክቶች ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ በስርዓታችን ውስጥ ያለው ትልቁ የልማት አቅም በክልሎች የሚገኝ እንደሆነና ክልሎችን የሚያስተዳድሩ ብሄራዊ ድርጅቶች የየክልላቸውን የልማት አቅም አሟጠው የሚጠቀሙበትን ሁኔታ መፍጠር እንዳለባቸው ሥራ አስፈፃሚው በአጽንኦት አስምሮበታል፡፡ በተጨማሪም ሃገራዊ አንድነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን ከሕዝብና ከመንግሥት ጋር በመሆን ማከናወን እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
  4. የመንግሥት መዋቅሩ ለሕዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት እንዲችል ለማድረግ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግና መስተካከል ያለባቸው አቅጣጫዎች እንደገና ከሕዝባችንና ከፈፃሚ አካላት ጋር በመሆን ተከልሰው ሙሉ ትግበራ ውስጥ እንዲገባ ተወስኗል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በፌዴራልም በክልልም ያለው ሲቪል ሰርቪስ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የአገልጋይነት መንፈስ የሕዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ እንዲረባረብ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
  5. በአገራችን የተመዘገቡት ስኬቶች ዋነኛ ሚስጢር የሕዝብን ተሣትፎ ማረጋገጥ መቻሉ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የሕዝብን አመኔታ መልሶ ለማግኘትና ለህዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ተከታታይ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ ወስኗል፡፡ ሕዝብ የሚደመጥበትና ወሳኝነቱ በሚገባ የሚረጋገጥበት እድል እንዲሰፋ አፅንኦት ሰጥቶታል፡፡ በተለይ ደግሞ ወጣቶቻችን የሚያነሱዋቸውን ጥያቄዎች በሚገባ ለመመለስና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና በልማት ሊኖራቸው የሚገባውን ተሣትፎ በተሟላ መልኩ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተከታታይ ሥራዎች እንዲሰሩ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡
  6. በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን ከሁሉም ተቃዋሚ ድርጅቶችና ከህዝቡ ጋር በመሆን ለመቅረፍ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ወስኗል፡፡ ምሁራንና የሲቪክ ማህበረሰቦች ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ተገቢ ሚናቸውን የሚጫወቱበት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ወስኗል፡፡
  7. ህገመንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን ያስከበራቸውን ሰብዓዊና ዴሞከራሲያዊ መብቶች የመጣስ አዝማሚያዎችና ተግባራት በጥብቅ እንዲመከቱ ወስኗል፡፡ በዚህ ረገድ የሕዝብን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በአስተማማኝ ደረጃ ለማስከበር ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ተጨማሪ እርምጃዎች እንዲወሰዱም አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
  8. በልማትና በሃገራዊ አንድነት ዙሪያ መትጋት ሲኖርባቸው ሕዝብን ከህዝብ ጋር በሚያራርቅ አፍራሽ ተግባር ውስጥ የተሰማሩ የግልና የመንግሥት የሚዲያ ተቋማት አካሄዳቸውን የሚያስተካክሉበት ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚንቀሳቀስ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የወሰነ ሲሆን በተለይም በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ ከፖለቲካዊ፣ ከሕጋዊ አሠራርና ከሕገመንግሥታዊ ሥርዓት በራቀ መልኩ የሁከትና የግርግር መልዕክት በህዝብ ሚዲያ የሚሰበክበትን ዕድል ለመዝጋት የሚያስችሉ የተቀናጁ እርምጃዎችን እንደሚወስድ በዚህ አጋጣሚ ይገልፃል፡፡

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች፣ ምሁራን፤ የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች፣ አጋር ድርጅቶች እንዲሁም የፀጥታና የህግ አስከባሪ አካላት

ድርጅታችን ኢህአዴግ ለአለፉት 26 ዓመታት በእናንተ በመተማመንና ከእናንተ ጋር እጅ በእጅ በመተሳሰር ለመብታችሁና ጥቅማችሁ መከበር የምትበቁባት አገር መገንባት ጀምረናል፡፡ በዚህ ሂደት የከፈልነው መስዋዕትነት ከባድ እንደነበረው ሁሉ ከሩብ ምዕተ ዓመታት በላይ የዘለቀ ለውጥ ለማስመዝገብ ችለናል፡፡ ምንም እንኳ በዚህ አጭር ጊዜ ሁሉም ችግሮቻችን ተሟልተው ይቀረፋሉ ተብሎ መጠበቅ ባይቻልም በተመሳሳይ የእድገት ደረጃ ከሚገኙ አገሮች በላቀ ፍጥነት ተጉዘን አገራዊ ትንሳኤያችንን ማረጋገጥ ጀምረናል፡፡ የአገራችን የወደፊት ዕድል የሚወሰነው የጀመርነውን የህዳሴ ጉዞ ጠብቀን ድሎቻችንን በማስፋትና ድክመቶቻችንን አርመን ዳር ለማድረስ ስንችል ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም የአጋጠሙንን ጊዜያዊ መሰናክሎች ሁሉ በፅናት ተፋልመን ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ ድሎቻችንን ለማስፋት የተለመደ ድጋፋችሁና ወሳኝ እንቅስቃሴያችሁ እንዳይለየን፤ በአጠፋንበት እያረማችሁ፣ በአጎደልንበት እየሞላችሁ አገራችንን ተባብረን እንድንገነባ የኢህዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

ታህሳስ 21 ቀን 2010 ዓ.ም

Published in ፖለቲካ

ኢትዮጵያ በዓለም ሰፊ የብዝሀ ህይወት ክምችት ካለባቸው አገራት መካከል አንዷ ለመሆኗ በርካቶች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ። ከእነዚህ መካከልም እ.ኤ.አ በ1960 የራሽያ እጽዋት ተመራማሪ የሆነው ቫቭሎቭ የሰጠውን ምስክርነት ማንሳት ይቻላል። ይህ ተመራማሪ በዚህ ዙሪያ በዓለም ላይ በርካታ አሰሳዎችን አድርጓል። እናም አገሪቱ በሰብል ተለያይነትና መገኛ ምንጭነት ከታወቁት ስምንት አገሮች መካከል አንዷ መሆኗን አስቀምጠዋል። የአየር ጸባይ ምቹነት፣ በአፈር ዓይነትና የተለያየ ሥነ ምህዳር ባለቤት በመሆኗ ደግሞ ለበዙት ብዝሃ ህይወት መገኛነቷ እንደምክንያት አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ካላት ባህልና ቋንቋ አንጻርም የተለያየ የአገረሰብ እውቀት ያላት መሆኑን እንዲሁ የሚናገሩት ተመራማሪው፤ በዘርፉ ከሚከናወኑት ተግባራት ጋር ተዳምሮ የአገሪቱ ብዝሀ ህይወት እንዲበራከትና እንዲጠበቅ ያደረገው መሆኑን ያስረዳሉ።

ይህ እውነት እንደተጠበቀ ሆኖ ግን፤ አሁን ላይ ይህ የብዝሀ ህይወት ብዛት እየተመናመነ እንዲሄድ የሚያደርጉ በርካታ ችግሮች እየገጠሙት እንደሚገኝ ሰሞኑን በቢሸፍቱ ከተማ የኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ኢንስትቲዩት ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ተነግሯል፡፡ ችግሩን ለማቃለልም ኢንስቲትዩቱ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ቢሆንም፤ በአንድ ተቋም ብቻ የሚደረግ ጥረት የሚፈለገውን ውጤት ስለማያስገኝ ባለድርሻዎች ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማርዮ እንዳሉት፤ የብዝሀ ህይወት በዘላቂነት ተጠብቆ እንዲቆይ ኢንስቲትዩቱ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በዚህም በጥበቃ 90 የሚደርሱ አዝርዕት እና በሆርቲ ካልቸር፣ ከ80 ሺህ በላይ የሚሆኑ የደንና ግጦሽ መሬት ናሙና የወሰደ ሲሆን፤ ከአንድ ሺህ በላይ የደቂቅ አካላት ህይወትን ለማስከበር ችሏል።

ነገር ግን ሰዎች፣ የብዝሀ ህይወት መኖር ለኢንስቲትዩቱ ብቻ ሳይሆን ለአገር ብሎም ለአለም ህልውና ወሳኝ መሆኑን ካለመረዳት በብዝሃ ህይወት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ተግባራትን እንደሚያከናውኑ የሚያከናውኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህ ተግባር ደግሞ በእኔነት ስሜት ብዝሀ ህይወቱን የመጠበቅና የመንከባከብ ብሎም ለጋራ ተጠቃሚነት መስራት ላይ ብዙ ክፍተት መኖሩን አመላካች እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ተቋሙም ይሄን ችግር ለመከላከል እየሰራ መሆኑን በመጠቆምም፤ በተወሰነ መልኩ ቢሆንም የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እያከናወነ፤ ችግሮች እንዲፈቱም ከተቋማት ጋር ፕሮጀክቶችን በመያዝ እንዲተገበሩ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የብዝሀ ህይወት የሚጠፋባቸውም ሆነ በመጠኑም ቢሆን ችግር እንዲገጥመው የሚያደርጉ ጉዳዮች የአየር ንብረት ለውጥ፣ ሰው ሰራሽ አደጋዎች፣ መጤ ዝርያዎችና ህገወጥ አደን እንደሆኑ የሚገልጹት ዶክተር መለሰ፤ የመሬት ወረራና ከመጠን ባለፈ መልኩ መሬትን ለመጠቀም መሞከር እንዲሁም የተፈጥሮ አደጋዎች በዋናነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ያነሳሉ። በተለይ ማህበረሰቡ በአካባቢው የሚገኘውን የምርት ሁኔታ በመመልከት ብቻ ለነባር ዝርያዎች የሚሰጠውን ትኩረት እየቀነሰ መሆኑ ይህ ችግር እየሰፋ እንዲሄድ እንዳደረገው ይገልጻሉ፡፡

በአከባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር የተቀናጀ መሬት ገጽታ አስተዳደር የምግብ ዋስትና ስርዓተ ምህዳር ጥበቃ ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት ዶክተር ተስፋዬ ሀይሌ በበኩላቸው፤ ብዝሀ ህይወትን በዘላቂነት ጠብቆ ለማቆየት ከማህበረሰቡ ባለፈ ተቋማት ተቀራርበው በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ ይናገራሉ። በእርግጥ ኢንስቲትዩቱ፣ የብዝሀ ህይወት ሀብትን በመጠበቅ በዘላቂነት ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ፣ የዘረመል (ጄኔቲክ) ሀብት አቅርቦት እና ፍትሃዊ ጥቅም ተጋሪነትን በማስፈን ላይ አበክሮ ይሰራል። ሆኖም የኢንስቲትዩቱ ስራ ብቻ የሚፈለገውን ውጤት ሊያመጣ ስለማያስችል፤ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ተቀራርበው በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ብዝሃ ህይወትን ጠብቆ የማቆየት ስራ የአንድ ተቋም ኃላፊነት ብቻ ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት የሚናገሩት ዶክተር ተስፋዬ፤ ተቋማት ብዝሀ ህይወቱን ለመጠበቅ በችግሮቹ ዙሪያ በርካታ ተግባራት መከወን የሚችሉት ተባብረው በሚያከናውኑት ተግባር እንደሆነ ማመን ያስፈልጋቸዋልም ይላሉ። ለምሳሌ፣ ኢንስቱትዩቱ ብዝሀ ህይወትን የመጠበቅ ስራ ሲያከናውን የግብርና ምርምር ደግሞ ምርታማነቱን ላይ ሊሰራ ይገባል፡፡ ከዚህም ባለፈ ነባር ዝርያዎችን ለማቆየት ትኩረት አድርጎ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ነገር ግን ተቋማቱ ለብቻቸው ያለባቸውን ኃላፊነት ብቻ እየተወጡ በመሆኑ በብዝሀ ህይወቱ ላይ ችግር ማጋጠሙ አይቀሬ ነው።

እንደ ዶክተር ተስፋዬ ገለጻ፤ የተቋማት ስራ የጎንዮሽ ችግሮችን በሚያይ መልኩ መስራት ይኖርበታል፡፡ ይህን መሰረት በማድረግ በመጠኑም ቢሆን ብዝሀ ህይወት አብሮ በቅንጅት የሚሰራባቸው ተቋማት አሉ። በሚፈለገው ልክ ባለመሆኑ ግን የሚጠበቀውን ለውጥ ማምጣት አልተቻለም፡፡ ዝርያን ማሻሻል እና በነበሩበት ሁኔታ ማቆየት የተለያዩ ጉዳዮች እንደመሆናቸውም ተቀናጅቶ መስራት ካልተቻለ በብዝሃ ህይወት ዘላቂነት ላይ ችግር መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ስለሆነም ተቋማት ይህንን በመገንዘብ ተናበው ሊሰሩ፤ ማህበረሰቡም ለዘላቂ የብዝሀ ህይወት ጥበቃ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡

በአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር በብዝሃ ህይወት ጥበቃ ስራዎች ማበረታቻዎችን ማካተትና የስርዓተ ምህዳር አገልግሎት ክፍያ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አብደታ ደበላም በዶክተር ተስፋዬ ሀሳብ ይስማማሉ። በተለይ በብዝሀ ህይወት ጥበቃ ላይ ለመጡ ችግሮች ዋነኛ መንስኤው የተቋማት ተባብሮ ያለመስራት መሆኑን ያስረዳሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ ብዝሀ ህይወትን በርካታ ጉዳዮች ችግር ውስጥ ይከቱታል። ይሁንና ጥበቃው ዘላቂነትን እንዲያገኝ ከብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት ባለፈ አጋር ተቋም ተብለው የሚጠሩት አካላት ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ችግሩ እንዲፈታ እያመቻቹ ነው። በዚህም ለውጦች እየመጡ ሲሆን፤ በተለይ ጥበቃ ላይ ሥራዎቹ ጠንክረው እየተጓዙ ነው። በፕሮጀክት ተደግፈው የማይሰሩት እንዳሉ ሆነው፡፡

በግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ብቻ ይህንን አድርግ ማለት ተገቢ አይደለም። ስለሆነም የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ እየተጠቀሙ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ይገባል የሚሉት አቶ አብደታ፤ በፕሮጀክታቸው ተጠቃሚነትን አረጋግጦ ጥበቃን ከማጠናከር አኳያ 144 ዶላር ተመድቦ በተወሰኑ ወረዳዎች ላይ እየተሰራ መሆኑን ይናገራሉ። ለውጦችም እየታዩ የመጡባቸው ወረዳዎች መኖራቸውን፤ ይህም ማህበረሰቡ ተጠቃሚነቱን እያየ እንዲሰራና ለብዝሀ ህይወቱ ልዩ ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያደርግ እንዳገዘው ያስረዳሉ።

በዚህ መልኩ የተከናወኑ ተግባራት ቦታዎች ተጠብቀው እንዲቆዩ ከግብርናው ወጣ ባሉ ተግባራት ላይ ተሳትፈው እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታ ይፈጠራሉ፡፡ ወረዳ ከወረዳ የሚለያይበትንና ነጥሮ የሚወጣበትን የምርት አይነት እንዲያለማ፤ በአንድ አይነት ዝርያ የሚሰማሩ አርሷደሮችን በተለያየ መልኩ የተመጣጠነ የምግብ አይነት እንዲያመርቱም እድሉን እንደሚያመቻችላቸው ነው አቶ አብደታ የሚናገሩት፡፡

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አርሶ አደር ቄስ ወንድም አማረ ግን ይህ ሁኔታ እንብዛም በሁሉም አካባቢ የሚከናወን አለመሆኑን ይገልጻሉ። በተለያየ አጋጣሚ ስልጠናዎችን ቢወስዱም ወደ ተግባር ለመግባት ሲያስቡ የሚነገራቸውና የሚተገበረው የማይገናኝ መሆኑን ደግሞ በምክንያትነት ያነሳሉ፡፡ በመሆኑም ሂደቱ ግንዛቤን ከማስጨበጥ ባለፈ በዛው ልክ ወደተግባር የሚቀየርበት ሂደት ላይ መስራት እንደሚገባም ይገልጻሉ፡፡ በተለይም የተቋማቱ ተናቦ ያለመስራትና ለራስ ፍላጎት የመቆም ሁኔታቸው አርሷደሩን እየተፈታተነው መሆኑን ነው የሚያስረዱት።

እንደ አርሷደር ቄስ ወንድም ገለጻ፤ አርሶ አደሩ በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እየተፈጠረለት ያለው ነገር አመለካከቱን እንዲቀይር ያደርገዋል። ለብዝሀ ህይወት ጥበቃም ልዩ ትኩረት እንዲቸርና ኢኮኖሚውን እንዲያሳድግ አወንታዊ ተጽዕኖ አለው። ነገር ግን  የፈለገውን ነገር አግኝቶ ተጠቃሚነቱ እየተረጋገጠ ካልሄደ መድረኮቹን ይንቃል፤ ባልገባው መስመርም እንዲጓዝ ይሆናል። በተለይም የተሻሉ ምርቶችን በማምረት ለአገርም ሆነ ለእራሱ የሚሆነውን አቅም ለማጎልበት እንዳይችል ሰፊ ክፍተት የሚፈጥር ነው። ስለዚህም ተቋማት ተናበው በመስራት የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳያጋጥም፤ በዚያ ላይ ሥራዎች በምን መልኩ መከወን እንዳለባቸው ማስረዳት ይገባል።

ለአብነት የተሻሻሉ ምርቶች መጥተዋል ተጠቀሙ ሲባል እንደ አካባቢው ሁኔታ ያንን ተቀብሎ እየሰራ ቆይቶ አሁን የለም ቢባል ያ አርሷደር ጦሙን ያድራል። ይህ ሆነ ማለት ደግሞ አገሪቱም ችግር ውስጥ ትወድቃለች ነው። ስለዚህ የሚወራውና የተቋማት መናበብ እንዲሁም መሬት ላይ ያለው ሁነት ተናቦ እንዲሰራበት የማድረጉ ሁኔታ የተማረው ኃይልና የተቋማቱ ኃላፊነት ስለሆነ ልብ ሊሉትና ሊሰሩበት እንደሚገባ አበክረው ይናገራሉ።

የፕሮግራሙ ተሳታፊና ከቱሪስት ድርጅት የመጡት አቶ ሲሳይ ኃይሉ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ዛሬ ላይ ነባር ዝርያዎችን ማግኘት በጣም ከባድ እየሆነ መጥቷል። ምክንያቱ ደግሞ ነባሮቹ መዳቀላቸው፤ አዳዲስ ዝርያዎች መገኘታቸው ሲሆን፤ ምርት እንጂ ጣዕምና ጤንነትን የሚያጎናጽፉ ሆነው አይታዩም። ለዚህም ማሳያው በትውልዶች መካከል እየታየ የመጣውን የአካላዊ ጥንካሬ ለውጥና በሽታን የመቋቋም አቅም መመልከት በቂ ነው። ስለሆነም ነባር ዝርያዎችን ማቆየትና መጠበቅ ላይ መስራት ያለበት ኢንስቲትዩቱ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዜጋ ነው።

ተቋማትም ቢሆኑ ለእነዚህ ብዝሀ ህይወቶች ጥበቃ ልዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው። ምክንያቱም ዘሮቹ እንደ አየሩ ጸባይና ሁኔታ፣ እንዲሁም እንደ መልከአምድሩ አቀማመጥ አበቃቀላቸውም ሆነ የዘር አያያዛቸውና በሽታን የመቋቋም ኃይላቸው ስለሚለያይ የሆነ ወቅት ችግር ቢከሰት ተመልሰው ሊጠቅሙ የሚችሉበት አጋጣሚ ሰፊ በመሆኑ ለነባር ዝርያዎች ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ባይ ናቸው።

ጽጌረዳ ጫንያለው

Published in ኢኮኖሚ
Monday, 01 January 2018 20:22

ከጥላቻ እንውጣ

በሀገራችን ባልተጠበቀ ሁኔታ እየተከሰተ ያለው ሁከትና ብሄር ላይ ያተኮረ ግጭት፤ ይህንንም ተከትሎ የሚስተዋለው አመጽ፣ ንብረት ማውደምና የሰው ሕይወት መጥፋትን የመሳሰሉ ቀውሶች መፈጠራቸው መንግስትንም ሕዝብንም ከልብ ያሳዘነ ድርጊት ሆኗል፡፡

ለዚህ ከመነሻው ጀምሮ የዚህ አይነቱ ግጭት እንዲነሳ ሆን ብለው በመስራት እልቂትና ደም መፋሰስ እንዲከሰት ሲጥሩ የነበሩ አንዳንድ አካላት የተጫወቱት ሚና ቀዳሚውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ለጉዳዩ መባባስና መልኩን ቀይሮ መከሰት የተጫወቱት የዘረኝነት ሚና፤ የረጩት የከፋ የጥላቻ መርዝ ሰውን በሰውነቱ፤ በዜግነቱ ከማየትና ከመመልከት፤ ለሰውኛ መብቱ ከመቆምና ከመከራከር ይልቅ የግለሰቦችን የግል አለመግባባትና ግጭቶች ሁሉ ወደ ጎሳና ብሄር እየለወጡ የተሳሳተ ትርጉም በማስያዝ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ እንዲወጡ ለማድረግ ይህ ቀረው የማይባል ጥረት አድርገዋል፡፡

ከአብሮነትና ከተለመደው ተከባብሮ የመኖር ኢትዮጵያዊነት ውጪ ሙሉ በሙሉ ባፈነገጠ መልኩ ለአንድ ዘር ወይንም ጎሳ ከእኛ በላይ ተቆርቋሪ የለም በሚል፤ የሌላውን ብሔር ብሔረሰብ በማጥላላትና በማንቋሸሽ ስሜታዊ ሆኖ ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዲሄድ የበቀልና የኃይል እርምጃ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ረገድ በየሶሻል ሚዲያው የተጫወቱት ሚና ሊገለጽ ከሚችለው በላይ ነው፡፡

ተው አደጋው ለሁሉም ይተርፋል፤ የሚበጀው በሰላምና በፍቅር አብሮ መኖር ነው ተብለው ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ቢነገራቸውም የሚሰሙ አልሆኑም፡፡ እንዲያውም ይህንኑ ነውረኛና ዘረኛ ስራቸውን እንደ ጀግንነት ቆጥረው በይፋ ድፍን ሕዝብ እስከ መዝለፍ መሳደብ የእኛ ዘር የተለየ ነው እስከማለት የደረሱ፤ ከጣሪያ በላይ የገዘፈ ጩሀት የሚያሰሙበት በአምሳያዎቻቸው አይዟችሁ የሚባሉበት ሁኔታ መከሰቱን ሁሉ ተመልከተናል፡፡ ቢያስቡ ኖሮ ሕዝብ ይከበራል እንጂ አይሰደብም፤ አይንቋሸሽም ነበር።

አንድ ሰው ሲበደል ግፍ ሲፈጸምበት ሰው በመሆኑ ብቻ ልንቆምለት ለመብቱም ልንከራከርለት ይገባል፡፡ ሁሉም የሰው ዘር በሕግ ፊት እኩል ነው የሚለው ብሔራዊም ሆነ አለም አቀፋዊ መርሕ ተገቢና ትክክለኛም ነው፡፡ ከእከሌ ጎሳ ከእከሌ ዘር ስለተፈጠረ ስለተወለደ የምንጠብቀው፤ ከሌላ ዘርና ጎሳ በመወለዱ በመፈጠሩ የምንጠላው የምናጠቃው ከሆነ ለሀገርም ለሕዝብም አብሮነት፤ ሰላምና መረጋጋት ትልቅ አደጋን ያስከትላል፡፡ አሁን የተከሰተው አካሄድም ይሄው ነው፡፡ ፈጥነን ተረባርበን ልንመክተው ካልቻልን በስተቀር፡፡

በሕዝብ ስም የሚነግዱ አንዱን ከአንዱ የሚያጋጩ ወንጀለኞች የመጨረሻው ግባቸው እልቂትና የእርስ በእርስ ግጭት ተፈጥሮ ሀገር ሰላምዋ ተናግቶ ሕዝቡ እንዲተላለቅ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ይሄ ደግሞ የኖረ የእነ ግብጽ የእነ ኤርትራ ቀዳሚ አላማና ኢትዮጵያን እንበታትናል ብለው ሲሰሩበት የኖሩት ሴራ ነው፡፡ሴራውም ኢትዮጵያን ለማጥፋት የታቀደ  ነው፡፡

በውስጥ ያለውና መፈታት ያለበት ሀገራዊ ችግር በውስጥ የሚፈታ ቢሆንም ይሄንን እንደ ማቀጣጠያ ነዳጅ በመጠቀም የራሳችንን ዜጎች በውስጥ በማሰለፍ በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ውስጥ ወኪሎችን በመመልመል የእርስ በእርስ የጎሳ ግጭት እንዲነሳ በተማሪዎች መካከል ግጭትና መጠፋፋት እንዲከሰት የሶሻል ሚዲያ ሠራዊት በማሰማራት ሰፊ ስራ እየሰሩ ያሉት ግብጽ ከኤርትራ ጋር በመቀናጀት ነው፡፡

ይሄንን የኖረና ግዜን ጠብቆ እየተከወነ ያለ ሀገር አጥፊ ሴራ ኢትዮጵያውያን በቅጡ ተረድተን ልንመክተው ካልቻልን ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ሴራ ሀገራችንን አሳልፈን ሰጥተናል ማለት ነው፡፡ ይህን ቀድሞ አውቆ መከላከል ሀገርንና ሰላምዋን መጠበቅ ጠላቶቻችን በዘረጉት ወጥመድ ተጠልፈን ሀገራችንን ለውደቀት ከመዳረግ መቆጠብ ይገባናል፡፡

የዘርና የጎሳ ፖለቲካ በሽታን ማስወገድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገሩ በየትኛውም ማእዘን ሰርቶም ሆነ ተምሮ ንብረት አፍርቶ ወልዶ ከብዶ ተዘዋውሮ የመስራት፤ የመኖር መብቱ እንደቀድሞው ሁሉ በፍቅር በመተሳሰብ በቤተሰባዊነት እንዲቀጥል ማድረግ መቻል አለብን፡፡ እርስ በእርስ በመናቆር፣ ሀገራችንን በማጥፋት ለግብጽና ለሻእቢያ ሴራ ሲሳይ መሆን የለብንም፡፡

አንድ ሰው ጥፋት  አጥፍቶ ቢገኝ መጠየቅ ያለበት በግለሰብነቱ ራሱ በፈጸመው ድርጊት እንጂ በጎሳው ወይም በዘሩ መሆን የለበትም፡፡ ይህ በየትኛውም አለም ሕግ የጸደቀና የሚሰራበትም ነው፡፡ ሕዝብ ከሕዝብ አይጋጭም፡፡ አይጠላላም፡፡ መነሻ ምክንያት የሚሆኑት ሁልግዜም በተሳሳተ መንገድ የሚራመዱ ግለሰቦች ናቸው፡፡ የግለሰቦች ስሕተትና ጥፋት እንደ ሕዝብ ጥፋት ሊታይ፤ ሊወሰድ የሚችልበት የሕግ መሰረትም የለም፡፡

ሰው ከእንስሳት ተለይቶ የማሰብና የማመዛዘን ባሕርይ ያለው ፍጡር ነው፡፡ መጠፋፋት፣ መበላላት፣ መገዳደል፣ ጎራ ለይቶ መፋጀት በተለይ የአውሬዎች አይነተኛ ባሕርይ ቢሆንም ምክንያታዊነት በሌለበት፣ ማስተዋልና ሚዛናዊነት በጠፋበት በጅምላ በስሜት መነዳት በሚነግስበት ወቅት ሰውም ልክ በሩዋንዳ እንደተፈጠረው የሁቱና የቱሲ ጎሳዎች ትርጉም በሌለው ሁኔታ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ እንደተላለቀበት የዘር ፍጅት አይነት  ሲፈጥር አይተናል፡፡

ከዚያ ሁሉ ሰቅጣጭ እልቂት ርዋንዳ በኋላ እንደገና ሀገሪቱ አንድ ብላ አቧራ አራግፋ ተነሳች፡፡ እንደገና ሕይወት ቀጠለ፡፡ ዛሬ ላይ ለምን ያ ሁሉ ሆኖ በፍቅር መኖር እያቻልን መቻቻል ተስኖን ነበር ብለው ቢጸጸቱም ያለቀውን ሕዝብ፣ የወደመውን ንብረት ሊመልሱት ግን አልቻሉም፡፡ የውጭ ኃይሎችም ያ ሁሉ እልቂት ሲፈጸም ፈጥነው በመድረስ ሊገቱት አልቻሉም፡፡ እንዲውም ዛሬ ላይ የነበራቸውን ሚና የሚገልጹ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ፡፡

ይህ አይነቱ  አስከፊና ዘግናኝ ሁኔታ በሀገሩ ላይ እንዲከሰት የሚፈልግ ማንም አይኖርም፡፡ በዚህ የከፋ ተግባር የተጠመዱትን ሕዝብን ከሕዝብ ማናቆር፣ ማጋጨትና ማባላት የሚፈልጉትን ከወዲሁ ሳይረፍድ ማስታገስ ተገቢ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲዎቻችን የተፈጠረው ሁከትና ተቃውሞ መነሻም ከዚሁ አይነት የብሄር ግጭት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ማንም ኢትዮጵያዊ በጎሳው በዘሩ ምክንያት ለጥቃት መዳረግና መሞት የለበትም፡፡ ይሄንን ያደረጉትን መንግስት ተከታትሎ ሕጋዊ ተጠያቂነትን ማስፈን መቻል ይጠበቅበታል፡፡ በአደባባይ ለፍርድ መቅረብም አለባቸው፡፡ ሌላው ሊማር የሚችለው በዚህ መልክ ብቻ ነው፡፡

የትምህርት ተቋማት እውቀት የሚቀሰም ባቸው አብሮ መኖር መቻቻል መተዋወቅ ማሕበራዊ ሕይወትን በጋራ መካፈል የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ልጆች በጋራ አንድ ማእድ የሚቆርሱበት እንጂ እጅግ ኋላቀር በሆነ የጎሳ ፖለቲካ መነሻነት የሚባሉበት መድረክ ከቶውንም ሊሆን አይገባውም፡፡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የሰው ልጅ ከምድር አልፎ ሕዋ ላይ ለመኖር እየታገለ ባለበት፣ ምጡቅ ቴክኖሎጂ በሰፈነበት ዘመን የዘርና የጎሳ ፖለቲካን ማቀንቀንን ቀዳሚ አጀንዳ ማድረጋችን ምን ያህል ከአለም ወደኋላ የቀረን መሆናችንን ያሳያል፡፡

ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ ክቡር ነው፡፡ በመሰረቱ ማንኛውም ሰው ከእከሌ ጎሳ ልወለድ ብሎ ማመልከቻ አቅርቦ የተወለደ በአለም ላይ የለም፡፡ ከየትኛው ዘር ጎሳ ይወለድ ሰው ሁሉ በእኩልነት ሰብአዊ መብቱ ሊከበርለት፤ ሊጠበቅለት ይገባል፡፡ ይህ የሞተ፣ ያረጀና ያፈጀ አስተሳሰብ ሀገርንና ትውልድን ይገድላል፡፡ በመሆኑም “ሳይቃጠል በቅጠል” ሊሆን ይገባልና ከወዲሁ ማሰብ ተገቢ ይሆናል።

ይልቃል ፍርዱ

Published in አጀንዳ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።