Items filtered by date: Wednesday, 10 January 2018

የቢቢሲ የወሬ ምንጭ በድረ ገጹ ባስነበበው ዘገባ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ847 ሺህ በላይ ስደተኞች አሉ። ይህ ቁጥርም ስደተኞችን በመቀበል ሃገሪቱን በአፍሪካ ሁለተኛ እንደሚያደርጋት የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን መረጃ ያሳያል። እነዚህ ስደተኞች አብዛኛውን ጊዜ ግጭትና አለመረጋጋት ካለባቸው እንደ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራና ሱዳን ካሉ ሃገራት ቢመጡም በአጠቃላይ የ19 ሃገራት ዜግነት ያላቸው ስደተኞች ናቸው።
ስደተኞቹ በአብዛኛው በትግራይ ክልል መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ያሉ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ተጠልለው ይገኛሉ። መረጃው እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ መንግሥት ከለላ ለሚፈልጉ ስደተኞች በሩ ክፍት እንደሆነ ነው። ይህንንም ለማድረግ ኢትዮጵያ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ፈርማለች። ብዙዎቹ ስደተኞች ያለውጣ ውረድ ወዲያው የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያገኛል። የእያንዳንዱም ስደተኞች ጉዳይ የሚወሰነው በኢትዮጵያ መንግሥት በተዋቀረ ኮሚቴ ሲሆን፤ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽንም በታዛቢነት ጉዳዩን ይከታተላል።
ሃገሪቱ በስደተኝነት የተቀበለቻቸውንም ሆነ ጥገኝነት ጠያቂዎች መንግሥት በመደባቸው የመጠለያ ጣቢያዎች መቀመጥ የሚኖርባቸው ሲሆን፤ ቁጥራቸው ብዙ ባይሆንም በከተማ ውስጥ እንዲኖሩ ፍቃድ የተሰጣቸውም አሉ። እነዚህም ከህክምና፣ ከደህንነት እንዲሁም ከሌሎች ችግሮች ጋር በተያያዘ ምክንያት መጠለያ ውስጥ መቆየት የማይችሉ ናቸው። በአዲስ አበባ ውስጥ 17ሺ345 ስደተኞች አሉ። ይህ የመንግሥት «ከመጠለያ ጣቢያ ውጭ» ከሚለው ፖሊሲ በተጨማሪ ኤርትራውያን ስደተኞች በአዲስ አበባም ይሁን በሌሎች ከተሞች ራሳቸውን ማስተዳደር ከቻሉ መኖር የሚችሉበት መንገድ ተመቻችቶላቸዋል። መንግሥት ከመጠለያ በተጨማሪ አትኩሮት የሚሰጥባቸው ጉዳዮች አሉ። እነዚህም ለህፃናት ስደተኞች ጥበቃ፣ ትምህርት፣ ወሲባዊም ሆኑ ፆታዊ ጥቃቶችን መከላከል ናቸው።
በተለይም ከኤርትራ ከቤተሰብ እገዛ ውጭ ብቻቸውን የመጡ ህፃናት በሽረ አካባቢ ለመንግሥትም ሆነ ለተለያዩ መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች አሳሳቢ እንደሆኑ እየተገለፀ ነው። የስደተኞች ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ ሲሆን በተለይም ከደቡብ ሱዳን ጦርነት ጋር ተያይዞ 2መቶ ሺህ የሚገመቱ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል። በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ያሉ የስደተኞችን ህይወት ለማሻሻል የተለያዩ ፕሮጀክቶችም እየተቀረፁ ነው።
ከእነዚህም መካከል ለወደፊት የተያዙት ዕቅዶች ከመጠለያ ውጭ ያሉ ቦታዎችን ማስፋፋትና ቢያንስ 10በመቶ ስደተኞች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ፤ ለስደተኞች የሥራ ፈቃድ መስጠት፤ የስደተኛ ልጆችን በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች እንዲሳተፉ ማድረግ፤ 10 ሺህ ሄክታር የሚታረስ መሬት 20ሺ ለሚሆኑ ስደተኞች መስጠትና የራሳቸውን እርሻ የሚያለሙበትን መንገድ መፈለግ እንዲሁም ከኢትዮጵያውያን ጋር በቀላሉ እንዲዋሃዱ የማስተሳሰር ፕሮግራም ይገኙባቸዋል።
በተያያዘ ዜና የሱዳን የፀጥታ ኃይሎች በከሰላ አካባቢ በሕገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ተይዘው የነበሩ ዘጠና ስምንት ኤርትራውያንን አስለቀቁ። ጊርባ በሚባል አካባቢ በሚገኝ የምሥራቅ ተሪንጋ ጫካ ውስጥ በሕገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ተይዘው የነበሩት 98 ኤትራውያንን ነፃ እንዳወጡ የምስራቅ ሱዳን የከሰላ አካባቢ የወንጀል ጉዳዮች ሃላፊ ብርጋዴር ጀነራል አብዱላሂ ኢል ሳይቅ ለሱዳን የዜና አገልግሎት በሰጡት መረጃ አረጋግጠ ዋል።
የማስለቀቅ ጥረቱ በተደረገበት ወቅት የፀጥታ ኃይሎቹ ከሕገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ጋር የተኩስ ልውውጥ የተደረገ ቢሆንም የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ተገልጿ። ከሕገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎቹ በኩል በርካታዎቹ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በሱዳን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ረዳት ሃላፊ መሀመድ ኢል ፋይዝ ናይም ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ ከሕገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎቹ እገታ ነፃ የወጡት ኤርትራውያን ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ድንበር ሲያቋርጡ ይሁን ወይም ተገደው የተያዙ መሆናቸውን ማረጋገጥ አልተቻለም ብለዋል። ሃላፊው ጨምረው እንደገለፁት እነዚህ ነፃ የወጡት 57 ወንዶችና 41 ሴቶች ሲሆኑ አምስት ህፃናት ከታገቱት ውስጥ ይገኙበታል። የጤና ሁኔታቸው እስከ አሁን በውል ባይታወቅም፤ ካሉበት አካባቢ ወዲ ሸሪፈይ ተብሎ ወደሚጠራ የስደተኞች መጠለያ ሲወሰዱ ያሉበትን ሁኔታ እንደሚጣራ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ አሁን ስለደህንነታቸው የሚያሰጋ ምንም ነገር የለም ተብሏል። ጉዳያቸውንም በሱዳን የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ይከታተለዋል ብለዋል። የከሰላ ዞን ባለስልጣናትም በዚህ ዓመት በአካባቢው የሚካሄዱ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና አፈናን ለማስቆም እንደሚሰሩ ገልጸዋል። የሱዳን መንግሥት በድንበሩ አካባቢ የሚካሄዱ ሕገ-ወጥ ተግባራትን በአግባቡ አልተቆጣጠረም በሚል በአሜሪካ መንግሥት ሲወቀስ ቆይቷል።
የሱዳን መንግሥት ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በተለያዩ አካባቢዎች የታፈኑ ኤርትራውያንን ከሕገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ነፃ በማውጣቱ ሲወደስ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያንን አስገድዶ ወደ ኤርትራ በመመለሱ በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሲወቀስ ቆይቷል።
በየዓመቱ ታህሳስ 9 በዓለም አቀፍ ዘንድ «የስደተኞች ቀን» በሚከበርበት በተለያየ ምክንያት ለተሰደዱ ህዝቦች በተለይም ከባዱ የሰሃራ በረሃንና ባህርን ተሻግረው የሚያርፉበት አገር የደረሱ ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን በስደት ያገኙትን አጋጣሚ በአግባቡ እንዲጠ ቀሙ መማር የሚችሉ እንዲማሩና ሰርተው ሊቀየሩ እንደሚገባ መምከሩ ይታወሳል።
ይሄንን ቀን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ አገራትና መንግስታት እና ተቋማት ውይይት ያደረጉ ሲሆን፤ በሊቢያ በረሃ በጨረታ የተሸጡትን ስደተኞች ትኩረት እንዲሰጡና መፍትሄ እንዲተገብሩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በአውሮፓውያኑ ታህሳስ 4/2010 ዓ.ም በስደተኞች ጉዳይ የመከረውና ታህሳስ 9 ዓለም አቀፋዊ ቀን ሆና እንዲከበር የወሰነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ1990 የሰራተኞችና ቤተሰቦቻቸውን መብት የሚከላከል ስምምነት አጽድቋል።
እየጨመረ የመጣውን ዓለም አቀፋዊ ስደት በጠንካራ ፖሊሲ እንዲደገፍ፣ መሰረታዊ ሰብአዊ መብቶች እንዲረጋገጡ እና ለስደተኞች የመንቀሳቀስ ነጻነት እንዲፈቀድ እና አህጉራዊና ከባቢያዊ መደጋገፍ እንዲሰፍንም 132 የድርጅቱ አባል ሃገራት የተቀበሉት ስምምነት ነው። ይሄንንም ተግባራዊ ማድረግ እንደሚ ያስፈልግም ባለታሪኮቻችን አፅንኦት ይሰጣሉ።

Published in ዓለም አቀፍ

 

ከቀናት በፊት በተከፈተው የጥር ወር የዝውውር መስኮት ከተፈፀሙ ዝውውሮች መካከል የሆላንዳዊው የመሃል ተከላካይ ቫንዳይክ በአነጋጋሪነቱ ጎልቶ ይጠቀሳል፡፡ የመርሲሳይዱ ክለብ ሊቨርፑል ቫንዳይክን ከሳውዛምተን ለማዘዋወር የተከላካዮችን የዝውውር ክብረወሰን በመስበር 75 ሚሊዮን ፓውንድ አውጥቷል፡፡ ብዙዎችን ግራ ያጋባው የሊቨርፑል ውሳኔ ለአንድ ተከላካይ እንዴት ይሄን ያህል ገንዘብ ያፈሳል? የሚለው ነው፡፡ ነገር ግን ሊቨርፑል በመግዛቱ ብቻ ሳይሆን በመሸጡም የተዋጣለት ይመስላል፡፡
ምክንያቱም በቀናት ልዩነት ውስጥ ቀያዮቹ ፍሊፔ ኮንቲንሆን ለባርሴሎና በመሸጥ ያጎደሉትን ካዝና በሚገባ መሙላት ችለዋል፡፡ ሆኖም እዚህ ጋር የሚነሳው ጥያቄ ግን ሊቨርፑል በፋይናንስ በኩል ያሳካውን ፈጣን ማገገም በሜዳ ላይ ለመድገም ይችል ይሆን? የሚለው ነው፡፡ እ.አ.አ 1970 እስከ1980 ለአስር ዓመታት በሊቨርፑል ማሊያ በተከላካይ መስመር የተሰለፈው እንግሊዛዊው ፊል ቶምሰን፤ ሊቨርፑል የኮንቲንሆን ያህል ጥራት ያለው ተጫዋች ለማግኘት ረጅም ጊዜ እንደሚወስድበት ለስካይ ስፖርት ገልጿል፡፡
ኮንቲንሆ በባርሴሎና የሚኖረው ሚና ግልጽ ነው፡፡ ባለፈው ክረምት የስፔኑን ታላቅ ክለብ በመልቀቅ ለፈረንሳዩ ሀብታም ክለብ ፒ ኤስ ጂ የፈረመውን የኔይማር ቦታ የመሙላት ሚና ይኖረዋል፡፡ በእርግጥ ባርሴሎና የኔይማርን መልቀቅ ተከትሎ ፈረንሳዊውን ኦስማን ዴምቤሌ ከቦሩሲያ ዶርቱመንድ በዓለም ሦስተኛው ውድ ፈራሚ በማድረግ በ105 ሚሊዮን ዩሮ አዘዋውሯል፡፡ ይሁንና ዴምቤሌ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ለካታሎኑ ክለብ ድንቅ ብቃቱን በሜዳ ላይ ሊያሳይ አልቻለም፡፡ አሁን የኮንቲንሆን ወደ ክለቡ መቀላቀል ተከትሎም ምንም እንኳን በአሰልጣኙ ታክቲክ ቢወሰንም ዴምቤሌ በሜዳ ላይ የመሰለፍ ስጋት በተጨማሪ የዓለም ሦስተኛ ውድ ፈራሚነቱንም ለኮንቲንሆ አስረክቧል፡፡ ምክንቱም የኮንቲንሆ የዝውውር ዋጋ ከዴምቤሌ በ55 ሚሊዮን ዩሮ ይበልጣልና፡፡ የሆነው ሆኖ በዓለም የክለቦች እግር ኳስ ታሪክ ክለቦች ትናንሽ ቀዳዳዎቻቸውን ለመሙላት ከሚያከናውኑት ዝውውር በስተቀር ብዙ የማይደፈረው የጥር የዝውውር መስኮት ገና ከአሁኑ በአንድ ክለብ ብቻ ከሁለት መቶ ሚሊዮን ዩሮ በላይ ለማንቀሳቀስ ችሏል፡፡
ኮንቲንሆ የዓለማችን ውዱ ፈራሚ በሚለው ሰልፍ ላይ በሦስተኛ ደረጃ ተቀምጧል፡፡ በዚህ አሰላለፍ ኔይማር በ222 ሚሊዮን ዩሮ በቀዳሚነት ሲቀመጥ፤ የፒ ኤስ ጂ አጋሩ ኬይሊዬን ምባፔ በ180 ሚሊዮን ዩሮ በሁለተኛነት ደረጃ ይዟል፡፡ ሃያ ያህል ቀናት በሚቀረው የጥር ወር የዝውውር መስኮት ከአርሰናሉ አሌክሲስ ሳንቼዝ እስከ ሞናኮው ቶማስ ሌማር ድረስ ብዙ ዝውውሮች ተጠባቂ ሆነዋል፡፡ እስከዚያው ግን የጥር ወር የዝውውር መስኮት ከወዲሁ በቫንዳይክና በኮንቲንሆ ዝውውሮች መሟሟቅ ጀምሯል፡፡

ብሩክ በርሄ

Published in ስፖርት

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚዎችና የፕሬዚዳንት ምርጫ እንዳወዛገበ ቀጥሏል፡፡ በቀረቡት እጩዎች መካከል የነበረው የምረጡኝ ዘመቻ ፤አንደኛው ሌላኛው ጥሎ ለማለፍ የሚያደርገው ጥረት ቀላል አይደለም፡፡ ሽኩቻው በስፖርቱ ዘርፍ አነጋጋሪና አደናጋሪ ክስተት ሆኖ መዝለቁን ብዙዎች ይስማማሉ።
ፌዴሬሽኑን ለቀጣዩ አራት ዓመታት ለመምራት ለእጩነት በቀረቡት ተፎካካሪዎች መካከል የነበረው ሽኩቻና የምርጫ ቅስቀሳ ትዝብትን መጣሉም አልቀረም፡፡ በውዝግብ የታጀበውና በተለያዩ ምክንያቶች መርሀ ግብሩ የተራዘመው ምርጫ መቋጫውን ሊያገኝ ጥር 05 ቀን 2010 ዓ.ም ቀን ተቆርጦለታል፡፡
ምርጫው ሰዎችን በሰዎች ለመተካት ሳይሆን እየሞተ እንደሆነ የሚነገርለትን እግር ኳስ ለመታደግ መሆን እንዳለበት አስተያየታቸውን የሚሰጡ የስፖርቱ ቤተሰቦች ይናገራሉ፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ በተለይም ባለፉት አራት ወራት እና ከዛ በፊት በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ፣ በቻን ማጣሪያ እንዲሁም በኬንያ አስተናጋጅነት በተካሄደው የምስራቅ እና መካከለኛው ምስራቅ አገራት ዋንጫ (ሴካፋ) የነበረውን ተሳትፎ መመልከት እግር ካሱ አደጋ ውስጥ ለመውደቁ ጥሩ ማሳያዎች ናቸው፡፤
በብሔራዊ ቡድኑ የተመዘገቡት ዝቅተኛ ውጤቶችና ደካማ አቋም በአመራሩ ምርጫ ውዝግብ ተሸፋፍኖ ሊያልፍ ችሏል፡፡ እናም በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የተመራው ዋልያዎቹ ከተሳትፎ ያላለፈ ውጤት አስመዝግቦ አልፏል፡፡ በምርጫ ሽኩቻ ውስጥ የከረመው አመራር ግን ይህን ጉዳይ ዞር ብሎም እንዳልተመለከተው የሚናገሩ በርካታ ናቸው፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ አመራሩ ትልቁ ትኩረቱ ምርጫው ሆኗልና የሚል ነው፡፡
በቅርቡ ብሄራዊ ቡድኑን ላለፉት አስር ወራት ሲያሰለጥኑ የቆዩት አሸናፊ በቀለ በራሳቸው ፈቃድ ከአሰልጣኝነት ለቀዋል፡፡ አሰልጣኝ አሸናፊ ከብራዊ ቡድኑ ለመልቀቃቸው የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም ባለፉት አስር ወራት የብሄራዊ ቡድኑ ውጤት ዝቅተኛ መሆን ሚዛን ይደፋል፡፡
ስፖርቱን ለመምራት የሚደረገው ትልቅ ሽኩቻ ጥረት መቃብር አፋፍ ላይ የደረሰውን እግር ኳስ ለመታደግ መሆን እንዳለበት ነው የስፖርት ቤተሰቡ የሚናገረው፡፡ ተፎካካሪዎቹ ይህን ዓላማ ይዘው ከሆነ ትልቅ የቤት ስራ እንደሚጠብቃቸው ሊገነዘቡ እንደሚገባ የሚያሳስቡ አሉ፡፡ ለዚህ እንዲረዳም እግር ኳሱን ወደ ፊት ሊያራምድ የሚችል ዕቅድ ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይም ብሄራዊ ቡድኑን በአፍሪካና በሌሎች ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ለማብቃት የሚደረገው ጉዞ ትልቁ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው።
ብሔራዊ ቡድንን ለውጤት በማብቃት ረገድ አሰልጣኞች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ለብሔራዊ ቡድኑ ውጤታማነትና ደካማነት ከማንም በላይ አሰልጣኙ ነው የሚጠየቀው፡፡
እናም ለብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት የሚመረጡ ግለሰቦች ይህን ኃላፊነት በደንብ ተረድተውና ተገንዝበው ሊሆኑ እንደሚገባ ይነገራል፡፡ ኃላፊነቱን ለመወጣትም ቁርጠኝነቱ ሊኖራቸው ግድ ይላል፡፡
ብሄራዊ ቡድኑ ከ31 ዓመት በኋላ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እየተመራ በአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ መብቃቱ እንደታሪካዊ አጋጣሚ እየተወራ ይገኛል፡፡ ከደቡብ አፍሪቃው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ በኋላ የዋልያዎቹ ጉዞ ቅጥ አንባሩ እንደጠፋ የሚናገሩ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡
የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በህንዳዊው አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ እንዲተኩ ተደረገ። ማሪያኖ ባሬቶም ቡድኑን ተረክበው ለአፍሪካ ዋንጫ እንደሚያበቁ ቃል ገብተው ሥራቸውን ጀመሩ፡፡
አሰልጣኙ ወደ ብሄራዊ ቡድኑ ሲመጡ የአገሪቱን የስፖርት መሰረት ጠንቅቀው ያውቁ ነበር ወይ የሚለው ጉዳይ ሳያነጋግር አላለፈም፡፡ ባሬቶ በሰውነት ቢሻው የተገነባውን ቡድን በማፍረስ በአዲስ ተጫዋቾች ቡድኑን አዋቀሩት። የብሄራዊ ቡድን ልምድ ያልነበራቸውን በማሰለፍ ልምድ ያላቸውን ከምርጫ ውጪ አደረጉ። እርምጃው የማይዋጥላቸው አካላት ‹‹ ምን አዲስ ነገር አመጡ ከሚለው ጥያቄ ለመዳን እንጂ ልምድ ያለውን ተጫዋች ከወጣቱ አጣጥሞ መሄዱ ጠፍቷቸው አይደለም›› ይላሉ፡፡
በዚህም ጉዞውን ወደ ፊት መግፋት ያቃተው ብሔራዊ ቡድን ለሌላ አሰልጣኝ በሩን ከፈተ፡፡ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ዋልያዎቹን ተረከቡ። እሳቸውም ቢሆኑ ታዲያ ውጤት ለተራበው የኢትዮጵያ እግር ኳስ አፍቃሪ ያመጡት ነገር የለም፡፡ አሰልጣኝ ዮሀንስን በጊዜያዊነት የተኩት አሰልጣኝ ገብረ መድህን ኃይሌ ቋሚ አሰልጣኝ እስኪቀጠር ድረስ ዋልያዎቹን በጊዜያዊነት ማሰልጠኑን ተያያዙት፡፡ በመጨረሻም በቅርቡ የተሰናበቱት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ዋልያዎቹን ተረከቡ፡፡
አሰልጣኝ አሸናፊ ዋልያዎቹን ከመረከባቸው በፊት ቡድኑ መያዝ ያለበት በአገር ውስጥ ወይስ በውጭ አሰልጣኝ የሚል ክርክር ተነስቶ ነበር። ይህን ተከትሎ የስፖርቱ ማህበረሰብ የዘረፉ ባለሙያዎችና መገናኛ ብዙኃን ትልቁ ነገር ቀለምና ዘር ሳይሆን ቡድኑን ውጤታማ የሚያደርግ አሰልጣኝ መቅጠሩ ላይ ነው በማለት ሃሳባቸውን አንሸራሽረዋል፡፡
በመጨረሻም መጋቢት አንድ ቀን 2009 ዓ.ም አሸናፊ በቀለ ዋልያዎቹን በይፋ ተረከቡ፡፡ በ100ሺህ ብር ወርሃዊ ደመወዝ ሥራቸውን ጀመሩ፡፡ በተቀመጠው ቅድመ ሁኔታም ዋልያዎቹን ለቻን እና ለአፍሪካ ዋንጫ፣ እንዲሁም በአፍሪካ ዋንጫ እስከ ሩብ ፍፃሜ አደርሰዋለሁ በማለት ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡ ይህ ካልተሳካ ግን ቀደም ብለው ሥራቸውን እንደሚለቁ አስታወቁ፡፡
የተገባውን ቃል ተግባራዊ መሆን የተጠራጠሩ በርካቶች አጉረመረሙ። የጋዜጣው ሪፖርተርም በወቅቱ አሰልጣኙን በስልክ አነጋግሯቸው የገቡትን እንደሚፈፅሙ አረጋግጠውለታል፡፡
የተገባው ቃል ተግባራዊ ላለመሆኑ ጥርጣሬው የተነሳው ከአሰልጣኙ ችሎታ ጋር በተያያዘ አልነበረም። ይልቁንም ብሔራዊ ቡድኑ በወቅቱ የነበረው ነጥብና አቋም ይሄን ለማሳካት የሚያስችል አልነበረም። ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ አሰልጣኙ ብሄራዊ ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ በማብቃት ከሩብ ፍፃሜ አደርሳለው ሲሉ ዋልያዎቹ የመጀመሪያውን ማጣሪያ በአሰልጣኝ ገብረመድህን እየተመሩ አከናውነው ነበር፡፡ የወቅቱም ውጤት ብሄራዊ ቡድኑ ከጋና ጋር የሚጠብቀውን ጨዋታ ማሸነፍ የግድ ይለው ነበር።
እነዚህ እውነታዎች እንዳሉ ሆነው ለወራት ያለ አሰልጣኝ የቆየና ዝግጅት ያላደረገን ቡድን በመረከብ ጋናን በማሸነፍ ለአፍሪቃ ዋንጫ አበቃለሁ ብሎ ቃል መግባት የማይታሰበ እንደሆነ ነው ብዙዎች የሚያነሱት፡፡ የስፖርቱ ማህበረሰብና የዘርፉ ባለሙያዎች ይህን ስጋት ሲያነሱ ፌዴሬሽኑ ዝም ማለትን ነው የመረጠው፡፡ ምክንያቱም አሰልጣኙ እንዲህ ሲሉ ፌዴሬሽኑ በምን አግባብና መስፈርት ብሎ ሲጠይቅ አልታየም፡፡
ቃሉን ለመጠበቅ የመጀመሪያውን ጨዋታ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከጋና ጋር ለማድረግ ብሔራዊ ቡድኑን ይዞ ወደ ሜዳ የገባው አሰልጣኝ አሸናፊ አክራ ላይ በጋና 5ለ0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ተሸነፈ፡፡
ውጤቱን ተከትሎ ቀደም ሲል ቅሬታና ስጋታቸውን ሲያነሱ የነበሩ አካላት ከወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ያልተጣጣመ ዕቅድ ውጤቱ ከዚህ የዘለለ አይሆንም ሲሉ ተደመጠ፡፡ ፌዴሬሽኑ ቅጥሩን ሲያከናውን ለአሰልጣኞች ለሚያስቀምጠው መስፈርት የሚሰጠውን ምላሽ በአግባቡ የሚፈተሽ አለመሆኑን ያሳያል ይላሉ፡፡ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የቅጥር ሂደት ክፍተት ያለበትና ግልፅነትን የተከተለ አለመሆኑንም ነው የሚናገሩት፡፡
በአንድ ወቅት ከአሰልጣኝ ምርጫ ጋር ተያይዞ የቀድሞውን የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውን ቃለ መጠይቅ ባደረኩበት ወቅት «አሰልጣኝ የሚመጣው ለአገራችን ብሄራዊ ቡድን የሚጠቅም ነው መሆን የሚገባው። ከዚህ ይልቅ ተጠቅሞ ሊያስጠቅም የሚመጣ አሰልጣኝ ከሆነ.....» ብለውኛል፡፡ እናም አንድ አሰልጣኝ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በብቃት፣በጥራትና በታማኝነት ሊወጣ እንደሚገባ ነው አፅንዖት የሚሰጡት፡፡
ፌዴሬሽኑ አሰልጣኞችን ሲቀጥር ተገቢና ተጨባጭ መስፈርቶችን በማስቀመጥ፣ ግልፅነትና ተጠያቂነትን የተከተለ አካሄድ ቢከተል የተሻለ ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ አሰልጣኞችም የሙያው ስነ ምግባር የሚጠይቀውን ደንብ በማክበር ቢንቀሳቀሱ ውጤቱ ያማረ ሊሆን እደሚችልም ይጠቁማሉ-የስፖርቱ ቤተሰቦችና ባለሙያዎች፡፡
በብሄራዊ ቡድኑ ውስጥ በተደጋጋሚ የመመረጥ ዕድል ያገኘው ዳዊት እስጢፋኖስ፤የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ አመራረጥ ክፍተት እንዳለበት ይናገራል፡፡ አንድ አሰልጣኝ ወደ ብሄራዊ ቡድን ሲመጣ ይዞ ከሚመጣው እቅድ ባሻገር የዝግጅቱን ሁኔታ መሰረት ማድረግ እንደሚኖርበትም ነው የሚገልፀው፡፡ አሰልጣኞች ከተጫዋቾች ጋር በደንብ ለመግባባት የሚያስችላቸው በቂ ጊዜ እንዲያገኙ የጨዋታ ጊዜያት ከመቃረባቸው ቀደም ብሎ መቀጠር ቢገባቸውም ለጨዋታ 15 ቀን ሲቀር የሚቀጠሩበት አጋጣሚ መኖሩን ይናገራል፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ውጤት ይመጣል ብሎ መጠበቅ ተገቢነት የለውም ይላል፡፡
አሰልጣኝ አሸናፊ ከጋና ቀጥሎ ከጅቡቲ ጋር ያደረገው ለቻን ዋንጫ ማጣሪያን 5 ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ምንም እንኳን ጅቡቲ በእግር ኳሱ ያላት ታሪክ ከኢትዮጵያ ያነሰ ቢሆንም ውጤቱ እንደ መልካም ተቆጥሮ የመልሱ ጨዋታ ተጠበቀ፡፡ ጅቡቲ ቡድኑን በትኖ ለመልስ ጨዋታ ሳይመጣ ቀረ ተብሎ ፎርፌ ተገኘ።
ሁለተኛ የቻን የማጣሪያ ጨዋታ ከሱዳን ጋር ሀገር ቤት 1ለ1 በሆነ ውጤት ተለያዩ። ካርቱም ላይ ደግሞ ከሱዳን አቻው ጋር 1 ለ 0 ተሸንፎ ሱዳን በማለፉ የቻን ተሳትፎ ውሃ በላው። የተዘጋው የቻን ተሳትፎ ሌላ ዕድል በመገኘቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሩዋንዳ ጋር አዲስ አበባ ላይ ተፋለመ። ውጤቱ ግን ሩዋንዳ 3 ኢትዮጵያ 2 ሆነ፡፡ የመልሱን ጨዋታ ኪጋሊ ላይ በማድረግ 0ለ0 ተጠናቀቀ፡፡
በኬንያ አዘጋጅነት በተካሄደው የምስራቅ አፍሪካ አገራት ውድድር ሴካፋ ብሄራዊ ቡድኑ ያሳየው አቋም እጅግ የወረደ ነበር። በመጀመሪያው ጨዋታ ደቡብ ሱዳንን 3ለ0 ቢያሸንፍም በሁለተኛው ጨዋታ በብሩንዲ 4 ለ 1 ተሸንፏል፡፡ በሶስተኛው ጨዋታ ከኡጋንዳ ጋር 1ለ1 ተለያይቶ ከምድቡ ማለፍ ባለመቻሉ ተሰናበተ።
አሰልጣኝ አሸናፊ ከተለያዩ አራት አገራት ጋር ባከናወኑት የወዳጅነት ጨዋታዎች የአሸናፊነትን ድል ለመቀዳጀት አልታደሉም፡፡ በቦትስዋና 2ለ0፣ በሞሮኮ 4 ለ 0 የተሸነፉ ሲሆን ከዛምቢያ እና ከኡጋንዳ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይተዋል፡፡
በአሰልጣኝ አሸናፊ የሚመራው ቡድን ባለፍት 10 ወራት ባከናወናቸው 13 ጨዋታዎች በስድስቱ ሽንፈት፣ በአምስቱ አቻ ሲለያይ ጅቡቲና እና ደቡብ ሱዳንን በመርታት ሁለት የአሸናፊነት ታሪክን ፅፏል፡፡
አሰልጣኙ አጣብቂኝ ውስጥ ያለን ቡድን በመረከብ ከላይ የተገለፀውን ውጤት አስመዘግባለሁ ብሎ ቃል መግባቱ ተገቢነት እንዳልነበረው ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ፌዴሬሽኑም የተገባውን ቃል ያለማመንታትና መስቀለኛ ጥያቄ ዝም ብሎ መቀበሉ ለትዝብት መዳረጉ አልቀረም፡፡ የቅርቡን አነሳን እንጂ ቀደም ባሉት ዓመታትም ተመሳሳይ ችግሮች ይስተዋሉ እንደነበር ይታወቃል፡፡
የስፖርት ባለሙያው ዶክተር ኤሊያስ አቢሻክራ በበኩላቸው የብሄራዊ ቡድን ውጤት የማጣት ምክንያት የአሰለጣጠን ስርአቱና የአገሪቱ የስፖርት ሁኔታ አለመገናኘት እንደሆነ በአንድ ወቅት ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል። የአገሪቱን ስፖርት በሚገባ የሚያውቅ አሰልጣኝ ማምጣት የችግሩ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል::
የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የቅጥር ሂደት ብዙ እንደሚቀረው በርካቶች ይስማማሉ፡፡ ይህን ክፍተት መሙላትና ማስተካከል ያለበት ደግሞ ፌዴሬሽኑ ነው፡፡ አሁን ደግሞ የፌዴሬሽኑ አመራር ምርጫም ከሽኩቻ አልፀዳም፡፡ የምርጫው ዋዜማ ላይም ተደርሶ ከምርጫው ጋር በተያያዘ የግልፅነት ችግር እንዳለ ይነገራል፡፡ ይህ ሁሉ መራኮትና መሯሯጥስ ‹‹ቦታው ምን ስላለው ነው?›› የሚሉ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ እየተሰነዘሩ ነው፡፤
በተለያዩ ችግሮች ተተብትቦ የሚገኘውን እግር ኳስ ለመምራት ከፍላጎት በላይ ለውጥ የሚያመጣና እግር ኳሱን መታደግ የሚችል በተግባር ሊመነዘር የሚችል ዕቅድ መያዝ ይገባል፡፡
የፌዴሬሽኑ አመራሮች የምርጫ ፉክክር በሞት አፋፍ ላይ የሚገኘውን እግር ኳስ ለመታደግ መሆን አለበት፡፡ የምርጫ ውድድሩ የእግር ኳስ ውድድር ተሳትፎን በማሳደግ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ሊሆን ይገባል፡፡

ዳንኤል ዘነበ

Published in ስፖርት

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለ17 ቀናት ያካሄደው ስብሰባ ማጠቃለያ ላይ በአወጣው መግለጫ ዙርያ፣ በአጠቃላይ የስብሰባው ሂደት፣በተወሰኑ ውሳኔዎች ዙርያ የአራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች አመራሮች (የደኢህዴንና ኢህአዴግ ሊቀመንበር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣የብአዴን ሊቀመንበርና የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን፣የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል እና የኦህዴድ ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ) ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ከዚህ ማብራሪያ ስለወጣቶች፣ስለ መልካም አስተዳደርና ስለ ብሄራዊ ማንነትንና አገራዊነትን በሚመለከት ዙርያ የተሰጡትን ቀጣይ ማብራሪያዎች ይዘን ቀርበናል።
ወጣቶች
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ስለወጣቶች በሰጡት ማብራሪያ አገራችን የወጣቶች አገር ናት፡፡ ወደድንም ጠላንም አገራችን ሰባ በመቶ የሚሆነው ከሰላሳ ዓመት እድሜ በታች ነው። ከዚህ ውስጥ ህጻናትን እንኳን ብንቀንስ አርባ በመቶ የማይተናነስ ሥራ መስራት የሚችል በስራ ዕድሜ ላይ ያለ ወጣት አለ፡፡ አርባ በመቶ የሆኑ ሴትና ወንድ ወጣቶች በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የበኩላቸውን ድርሻ ካላበረከቱ በስተቀር ይሄ አገር የሚፈለገውን ፈጣን ልማትና ዕድገት ለማስቀጠል አይችልም፡፡ ስለዚህ ለወጣቶቹ ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ ዕድገትም ሲባል የወጣቶች ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ እንደሆነ በተደጋጋሚ የተወያይንበት ጉዳይ ነው፡፡ አሁን ጉዳዩ ወጣቶችን ራሳቸውን መስማት ፣ ልብ ትርታቸውን ማወቅ ፣ ማዳመጥ ያስፈልጋል፡፡ እነርሱ በጣም ብዙ ነገር በውስጣቸው አለ፡፡ ብዙ ፈጠራ በውስጣቸው አለ፤ ይሄን የፈጠራ ችሎታቸውን ዕውቀታቸውን ትምህርታቸውን ክህሎታቸውን ተጠቅመን ወጣቶች ለአገራችን ዕድገት የሚያበ ረክቱትን ከፍተኛ ሚና የሚመጥን አመራር ልንሰጥ ይገባል፡፡ እዚህ ላይ ያለን የአመራር ጉድለት በጣም ከፍተኛ እንደሆነ አይተናል፡፡ ስለዚህ ከወጣቶቹ ከራሳቸው ጋር ሆነን ልንቀርጽ የሞከርናቸውን ፓኬጆችን ጭምር አሁንም ቢሆን በሚገባ አሳትፈናቸው መስራት የሚገባን ይሆናል፡፡ እንግዲህ ወጣቶች የነገ ተስፋዎች ብቻ አይደሉም። የአሁኑ አገር ገንቢዎችም ናቸው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያችን ወደ ፊት ልትገሰግስ ከሆነ ከወጣቶች ውጭ ሊሆን የሚችል ነገር ይኖራል ተብሎ በጭራሽ ሊታሰብ አይችልም፡፡ እናም መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ አፅንኦት ሰጥቶ ሥራ እንዲሰራ በዚህ ላይ የተደራጁ ግብረ ኃይሎችም ጠንክረው መፈፀም እንደሚገባቸው እስካሁን ድረስ ያለውን ውጣ ውረድ ልናቃልል የምንችልበትን አመራር ልንሰጥ እንደሚገባን መተማመን የተደረሰበት ነው፡፡ ስለዚህ የወጣቶች ጉዳይ አሁንም ለእኛ የሞት የሽረት ጉዳይ ተደርጎ መወሰድ አለበት የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰናል ማለት ነው፡፡
አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው ከወጣት አኳያ ምናልባት አሁንም ቢሆን በግምገማችን በስፋት ታይቷል፡፡ አንዱ በጥንቃቄ መታየት ያለበት እዚያም እዚህም ግጭት ሲነሳ፣ የተለያዩ ጉዳዮች ሲነሱ የእነዚህ ወጣቶች እንደሆኑ አድርጎ የመሳልና የመገንዘብ ሁኔታ ብዙ ቦታ ያጋጥማል፡፡ ግን ወጣቶች የመፍትሄ አካል የሆኑ፣ ለውጡን ወደ ፊት ሊያራምድ የሚችል ትልቅ አቅምና ትልቅ ሀብት ናቸው፡፡ ወጣቶች ዛሬን ለመጠቀም፤ ዛሬ ያልተሟላና የጎደለው ነገር ለነገም ስለሚጎዳቸው በዚህ ደረጃ ለውጥን ከምንም በላይ ይፈልጋሉ፡፡ ተስፋ የሰነቁ ናቸው፡፡ ወጣቶች ፈጣን ምላሽ ይጠይቃሉ፡፡ ዘመኑ በፍጥነት እንድንራመድና እንድንጓዝ ያደርጋል፡፡ በዚህ አይን የወጣቶችን ሁኔታ በዝርዝር ማወቅና ፍላጎታቸውን ማዳመጥ ያስፈልጋል፡፡ ብዙ መፍትሄ ከእነርሱ ይንቆረቆራል፡፡ እንዲሁ ሰብስቦ በርቀት የማየትና የመፈረጅ አይደለም መፍትሄዎች ከእነርሱ አሉ፡፡ መፍትሄውን ራሳቸው በተግባር ሊመሩትና ሊፈጽሙት ይችላሉ፡፡ አቅሙ አለ።ተስፋው አለ። ትጥቁ አለ። ይህንን ሀብት በአግባቡ መጠቀምና በአግባቡ ማራመድ ያስፈልጋል፡፡ ማዳመጥ ይገባናል፤ መገንባት ይገባናል፤
የወጣት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ውስጥ እንዴት አድርገን ነው ይሄንን ወጣት የምናንቀሳቅሰው? ብሎ መስራት ተገቢ ነው።
ሌላው የወጣቶች ተሳትፎ በልዩ ልዩ መስክ በደንብ መታየት አለበት፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የወጣት ስብእና ግንባታ፣ በምንገነባው ስርአት ውስጥ የኢትዮጵያ ህዝቦችን ታሪክ በተሟላ ሁኔታ የማስገንዘብ፣ ያለፈ ታሪካችን ለአሁኑ እንደ ኩራት ምንጭ አድርገን እንደምንራመድበት፤ ካለፈው ታሪካችን ደግሞ ሊታረሙ የሚገቡ እንዲሁም አሁንም ሊደገሙና ልንሰራቸው የሚገቡ አሉ፡፡ እዚህ አካባቢ የምንሰራውን ስራ ማጠናከር ማስፋትና መማማር ይጠይቃል፡፡ በዚህ ላይ ተመስርተን ዴሞክራሲን ለመገንባት፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና የህዳሴውን ፕሮጀክት ወደ ፊት ለማራመድ ትልቅ ሀብት ወጣት ስለሆነ፤ ይህንን ለማጠናከር ምን እናድርግ ሲባል፤ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ከወሰነው አንዱ ቀደም ሲል በብሄራዊ ደረጃ የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያስተ ባብር ብሄራዊ ኮሚቴ ተደራጅቷል፡፡ እስከ አሁን ያለው አካሄድ አዝጋሚ ስለሆነ አሁን ባለው ፍላጎትና አገራዊ ሁኔታ የሚመጥን የብሄራዊ ኮሚቴ እንቅስቃሴ በፌዴራልና በክልል ተደራጅቶ ፖለቲካዊ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲመራና ወጣቶችም ከዚህ አኳያ የሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጠው ቁመና መላበስ አለበት ብለን ነው የያዝነው፡፡ አንድ የትኩረት መስክ ነው ለማለት ነው፡፡
መልካም አስተዳደር
አቶ ኃይለማርያም ደሳላኝ ስለ መልካም አስተዳደር ከመልካም አስተዳደር አኳያ ችግሩ እንዲፈታ ካስፈለገ የፖለቲካ አመራሩ አሁን በስራ አስፈጻሚ ደረጃ እንደታየው ግልጽነት ሁሉ በመላው ካድሬ እና አባሎቻችን እስከታች ድረስ መውረድ አለበት። እስከታች ድረስ በአንድ መንፈስ በአንድ ልብ ሆነን ከታገልን የመልካም አስተዳደር ችግር እየቀረፍን ልንሄድ እንችላለን። ለዚህ ደግሞ ወሳኙ አመራሩ በዚህ ደረጃ ከተስተካከለ ህብረተሰቡ ደግሞ የማይተካ ሚናውን እንዲጫወት ማድረግ የሚቻል ከሆነ ብቻ ነው። አለበለዚያ የመልካም አስተዳደር ችግር የመፈታቱ ጉዳይ ጊዜ መውሰዱ እና ችግሮች እየተባባሱ መሄዳቸው አይቀርም።
አንድ ተገልጋይ አገልግሎት ለመውሰድ በሄደበት ሁኔታ እኛ አገልግሎት ለመስጠት ያስቀመጥናቸው መስፈርቶች (ስታንዳርዶችን) አውቆ በተቀመጠው መሰረት አገልግሎት አልሰጠህም ሲባል በሙሉ ልቡ የማይታገል እና እንግልቱን ተቀብሎ የሚመለስ ከሆነ ችግሩን የማስተካከሉ ሂደት ዘገምተኛ መሆኑ አይቀርም። ስለዚህ በእኔ እምነት መንግስት ወይም ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ እራሱን ለማስተካከል የሚያደርጋቸው ጥረቶች እንዳሉ ከህዝቡ ደግሞ መልካም አስተዳደር እንዲጎለብት ለማድረግ የበኩሉን ሚና የሚጫወ ትበትን ሚና ያስፈልጋል። የሁለቱ ጥረት የመልካም አስተዳደር ስራችን ደረጃ በደረጃ እየተፈታ ይሄዳል የሚል ሙሉ እምነት አለ።
አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው በገጠርም በከተማም የመልካም አስተዳደር ችግሮች ምን ምን ናቸው? አሁንም ቢሆን በተቋም ፣ በስራ ዘርፍና መስክ ደረጃ ምንድናቸው? የሚሉትን የመለየት በእነዚህ ላይ ተመስርቶ ለውጡን ለማምጣት ያስችላሉ የተባሉት ለውጦችን (ሪፎርሞችን) አሟልቶ ተግባራዊ የማድረግ ስራ መስራት አለብን ብለን የመንግስት መዋቅራችን፣ ድርጅታችን ችግሩን በዝርዝር አይቶ በጠንካራ ቁመናው ወደ ንቅናቄው ሲገባ፣አንዱ እርምጃ የመንግስት መዋቅር ምላሽ ሰጭ ማድረግ፣ ተጠያቂ እንዲሆን፣ ለተገልጋዩ ህብረተሰብ በመርህ የተቀመጠውን በተግባር የሚተረጉም እንዲሆን የመንግስት መዋቅርን ማብቃት፣ ተጠያቂ ማድረግ፣ ለምናስበው ለውጥ ቁልፍ መሳሪያ እንዲሆን ማድረግ አለብን፡፡
ሌላው በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያለው የመንግስት ሰራተኛ በዚያ ዙሪያ ያሉበትን ችግሮች የመፍታት የአገልጋይነት ስሜቱን ተላብሶ የሚፈለገውን ተልእኮ እንዲወጣ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የእነዚህ ሁሉ ማጠንጠኛዎች መሪዎች ናቸው፡፡ መንግስት መዋቅርም አብዛኛውን ተቋምንም የሚመራው፣ ክልልም የሚመራው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ነው፡፡ እኔ በአግባቡ ስላልመራሁት በእነዚህ ችግሮች ውስጥ ተነክሬ ስለቆየሁ የመንግስት መዋቅርን ውጤታማ ማድረግ በሁሉም መስክ የሚፈለገውን እርካታ እንዳይረጋገጥ ስላደረግኩ መንግስት መዋቅርን ለዚህ ማዘጋጀት ያስፈልገዋል፡፡ አቅም ግንባታ ፣ የአስተሳሰብ ግልጸነት ፣ የክህሎት ትጥቅ ያስፈልጋል፤ የግንዛቤ እድገት ይጠይቃል፡፡ ይህን መሰረት ያደረገው አንዱ ከተዘረዘሩትና አሁን የስራ ክፍፍል ተደርጎ ስምሪት ከሚደረግባቸው ጉዳዮች አንዱ ይህን ማእከል ያደረገ ስራ መስራትና ውጤታማና ስኬታማ ስራ ማረጋገጥ አለብን ብለን ነው ያስቀመጥነው፡፡ ይህን አጠናክሮ መቀጠል ነው፡፡
ብሄራዊ ማንነትንና አገራዊነት
አቶ ደመቀ መኮንን ብሄራዊ ማንነትንና አገራዊነትን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ይህንን ከመገንባት አንጻር ክፍተት እንደነበረ ተለይቷል። ከዚህ አንጻር ባለፉት 25 ዓመታት የብሄር ማንነት ምን ያህል ለአገራዊ አንድነት ክፍተት እንዲፈጠር ሆኗል ብለው የሚያነሱ ወገኖች አሉና ይህ እውነት ነው ወደሚል ይወስደናል? ከዚህ ጎን ለጎን ከአሁን በኋላስ ለብሄር መብት ትኩረት አይሰጥም ወደሚል ነው የዚህ አገላለጽ ቅኝት የሚሆነው? ወይስ ምን ማለት ነው? ፡፡ ብሔራዊ ማንነትና አገራዊ ማንነትን አንድም ሁለትም ሆነው ከህገ መንግስታዊና ፌዴራላዊ ስርዓታችን ጋር አስተሳስሮ መመልከት በጣም ተገቢ ነው። በአገራችን ሁኔታ ከዓመታት በፊት የነበረው ሁኔታና ቅራኔ ምን ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር፣ ከዛ ሁኔታ ለመውጣት የተሠራው ሥራ እና የተገኘው ህገ መንግስታዊ ድል፤ የተረጋገጠው የብሔር እኩልነት እና በዛ ላይ ተመስርተን የገነባነው ብዝሃነት የአንድነት መሰረት እና ትልቅ ውጤት ነው።
ኢትዮጵያዊነት በጣም ጥልቅ ሃሳብ ነው። በእኛ አገር ሁኔታ ኢትዮጵያዊነት ጥልቅ ሃሳብነቱን የበለጠ ለማጠናከር በብዝሃነት ላይ የተመሰረተው አንድነት ለዚህ ጥልቅ ሀሳብ ትልቅ መሰረት ነው። ብዝሃነትን እንደ ጌጥ አድርጎ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በአካባቢያቸው ጉዳይ በሚመለከታቸው በእኩልነት ላይ ተመስርተው የሚጫወቱት ሚና በአገራዊ ጉዳይ ላይ ደግሞ በፌዴራል ስርዓት የሚጫወቱት ሚና በግልጽ ተቀምጧል።
ብዝሃነት በዚህ አገር ውስጥ ይህን ህገ መንግስታዊ ዋስትና አግኝቶ በተግባር ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በተግባር የተጓዝንበት ጉዞ ነው። የተዘረጋው መሰረት ለአንድነታችን እና ለኢትዮጵያ ዊነት ትልቅ መሰረት ነው ብሎ መነሳት ተገቢ ነው። የበለጠ ጥልቀት ይሰጠዋል። በዚህ ላይ ተመስርተን በብዝሃነት እኩልነት ከተረጋገጠ፤ የብሔር ጥያቄ ህገመንግስታዊ ምላሽ ካገኘ። ሁሉም አካባቢውን የሚመራበት የሚያስተዳድርበት፤ በአገራዊ ጉዳይ ላይ የሚጫወትበት፤ ሊጠቀም፣ በእድገቱ ውስጥ ሊተውን የሚገባውን ሂደት በተመቻቸበት ሁኔታ በዚህ መሰረት ላይ ቆመን ጠንካራ አገራዊነት መሰረቱ ተጥሏል። ይህ የበለጠ መሥራትና ማጠናከር ይኖርብናል።
የብሔር ማንነት ከዚህ አኳያ በመመለሱ ይህኛውን ጎድቷል ብለን ልንወስድ የምንችልበት በምንም መልኩ አይሆንም። በኢትዮጵያ ሁኔታ እንዲያውም ጥልቀት ያስገኘዋል። በዛ ላይ የተመሰረተው የአገራዊ አንድነት ግንባታ ግን ከመጣንበት ጉዞ ከደረስንበት ደረጃ አኳያ የበለጠ ሊጠናከርና ሊፋጠን የሚገባው ነው።
አንደኛ ቀደም ብለን ያልነው ከታሪክና አስተምህሮ አኳያ አንዳንድ ጊዜ በየአካባቢው በተመለሰው ህገመንግስታዊ ስርዓት በአካባቢ ላይ ያለንን እኩልነት መሰረት አድርጎ ወደ አገራዊ አንድነት ሊያራምዱን የሚችሉ እድሎችን ከመጠቀም ይልቅ የተለያዩ መንጠላጠያዎቹን በማንሳት ሁልጊዜ ያንን ታሪክ በመድገምና በመርገም፥ ሁለት አስርት ዓመታትን ከዛ በላይ እየተጓዝን የአዲሱ ፕሮጀክትና የአዲስ ኢትዮጵያን ግንባታ ማፋጠን ማጠናከር እየቻልን፤ እዛ አካባቢ ላይ የተሳሳቱ ዝንባሌዎችና አካሄዶች አሉ።
በሁለተኛ ደረጃ አሁንም በዚሁ ፌዴራል ስርዓታችን እና ህገመንግስቱ ብሔራዊ መግባባት ፋይዳው እና ምን መስራት እንዳለብን በዝርዝር ፖሊሲያችን ላይ ተቀምጧል፤ የብሔራዊ መግባባት ጉዳይ። ብሔራዊ መግባባት ከዳር እስከ ዳር ሁሉም በነቂስ እንኳ ሊላበሰው እና ሊይዘው ባይችል አብዛኛው በአስተሳሰብ ደረጃ ሊይዘው የሚችለው ምንድን ነው የሚለው ነገር ነው። በፌዴራል ስርዓት ውስጥ ከምንገነባው የልማትና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አንድ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ማኅበረሰብ እንዴት እንገንባ ተብሎ የተቀመጠ ጉዳይ አለ።
በዛ ላይ የተዘረጋውን እድል የተነጠፈውን መሰረት ማፋጠንና መገንባት ይጠይቃል። በብሔራዊ መግባባት ዙሪያ ሊጫወቱ የሚገቡ ተቋማትን የበለጠ እያሳተፉና ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወቱ፤ ካለው ታሪካችን አጉልተንና ለአሁኑ ትልቅ እሴት ሆኖ የሚሄደውን ይዘን የምንሄድበት፤ የሚታረሙት እንዳይደገሙ የምናደርግበት፤ የሚያጋምዱንን ገመዶች የበለጠ እያጎለበትን እነዚህን ሰበዞች ትልቅ ቦታ እየያዙ የሚሄድበትን እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል ማለት ነው።
በዛ ደረጃ የመጣንበት የጣልነው መሰረትና ስኬት አለ። በቂ ስላልሆነ ግን እንዴት አድርገን የበለጠ ትኩረት ሰጥተን እንጓዝበትና ትኩረት እንስጠው የሚለውን ነው እንጂ አንዱን ጥሎ አንዱን ይዞ መሄድ አይቻልም። ሁለቱም ይመጋገባሉ። በጽኑ መሰረት ላይ እየተገነባ፤ ጠንካራ አገራዊ አንድነት የበለጠ ሊጎለብት ይገባዋል። በተለያየ መልክ የሚነሳው ለብሔር ተኮር ሥራ ስለተሠራ ይህኛው ግምት እንዳይሰጠው ሆነ ማለቱ ከመሰረቱ ሊስተካከል የሚገባው ነው።
አቶ ለማ መገርሳ ደግሞ አንድነት እንዴት ይፈጠራል? የሚለውን ማየቱ ነው ጠቃሚ የሚሆነው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አገር ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አብዮቶችና ትግሎች ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡ እነዚህን ትግሎች መለስ ብለን ካየናቸው መሰረታዊ የሆኑ የብሄር ብሄረሰቦች ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ የነበረው አንድነት በውጫዊ ተጽእኖ የተፈጠረ የጭነት አንድነት በመሆኑ በመላው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ዘንድ ተቀባይነትን አላገኘም፡፡ ምክንያቱም የህዝቦችን ውክልና የማያሳይ አንድነት በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ብሄር ብሄረሰቦች ሲታገሉለት ከነበረው መሰረታዊ ጥያቄ ውስጥ አንዱ የብሄራዊ አንድነት ትልቁ ጉዳይ ነው፡፡ ከመሬት ጥያቄ ቀጥሎ የነበረው የማንነት ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ኢህአዴግ ብቻ ያመጣው ውጤት ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝቦችም ለዘመናት ለዚሁ መብት ሲያደርጉ የነበረው ትግል ውጤት ነውና ብሄራዊ ማንነት እንዲሁ ዝም ብሎ የተፈጠረ ጉዳይ ሳይሆን የህዝቦች ትግል ያመጣውና የፈጠረው ጉዳይ ነው፡፡ ይህም በዚህ ስርዓት እውን ሆኗል፡፡
እስከሚገባኝም ብሄራዊ ማንነታቸው ስለተከበረላቸው ብሄር ብሄረሰቦችም ደስተኞች ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን የሚያየው መጀመሪያ ከራሱ ነው፡፡ ከራሱ ማለት በኢትዮጵያ ውስጥ የእኔ ድርሻ ምንድነው? ይህች አገር ለእኔ ምንድነች? በዚህች አገር ውስጥ እኔ ማን ነኝ? ምንድነኝ? የሚሉ መሰረታዊ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ይህ ማለት ኢትዮጵያ ማንነት ከግለሰብ ነው የሚጀምረው፡፡ የግለሰብ ማንነቱ፣ የቡድንና የብሄር ማንነቱ ሲከበርለት ነው ኢትዮጵያዊነቱ በዚያ ውስጥ የሚከበርለት፡፡ ይህም በመሆኑ የብሄራዊ ማንነት ጥያቄ መመለሱ የህዝቦችን የዘመናት ጥያቄ የመለሰ የህዝቦች የትግል ውጤት ነው፡፡
ብሄራዊ ማንነት መመለሳቸው አገራዊ ማንነትን አልጎዳም ወይ ተብሎ የሚታየው እንደ ሰው አተያይ የተለያየ ትርጉም ሊሰጠው ይችላል፡፡ ነገር ግን በእኛ ሁኔታ የእያንዳንዱ ብሄረሰቦች የማንነት ጥያቄ መመለሱ ኢትዮጵያዊ አንድነትን የሚጎዳ አይደለም፡፡ እንዲያውም የበለጠ የሚያጠናክር ነው፡፡ ምክንያቱም ለመጀመሪያ ጊዜ ብሄር ብሄረሰቦች በኢትዮጵያ ውስጥ እውቅና ያገኙበት ጊዜ በዚህ ፌዴራላዊ ስርዓት ነው፡፡ እውቅና አገኙ ስንል የብሄራዊ ማንነታቸው መከበሩ ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ደግሞ ብሄራዊ ማንነታችንን ለማጠናከርና ለማጎልበት ስንሰራ አገራዊ አንድነታችንንም በማጠናከሩ ላይ መስራት አለብን የሚለው ግን አስፈላጊ ነጥብ ነው፡፡ አገራዊ አንድነቱ ተጎድቷል ከሚለው በላይ የበለጠ ማጠናከሩ ላይ መስራቱ ይጠቅመናል፡፡
የኢትዮጵያ አንድነት በምንም መልኩ ሊጎዳ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ማንም ሲፈልግ እንደ ገበያ አንድ ላይ የሚሰበስበው፣ ሲያሻው ደግሞ እንደ ገበያ የሚበትነው ነገር አይደለም፡፡ ብዙ ምስጢርና ታሪክ ያለው በኢትየጵያዊያኖች መካከል ብዙ የታሪክ፣ የማህበራዊ ህይወት ጉድኝትና ትስስር ያለው ማንም በቀላሉ የሚፈታው ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ ያለ ሀቅ ነው፡፡ ቢታሰብም የሚሆን ጉዳይ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ማንኛውም ሰው ግልጽ መሆን ያለበት ይመስለኛል፡፡
በሆነ አጋጣሚ የኢትዮጵያ አንድነት ሊፈርስ ሊበትን የሚችል የዝምብሎ ስብስብ አይነት አድርጎ የሚያይ አለ፡፡ ነገር ግን በእኔ እይታ በሁላችንም ግምገማ ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያዊ አንድነት ከምናስበው በላይ በብዙ ህይወት፣ በብዙ ኑሮ፣ ኢኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር የተዋሃደ ህዝብ ነው፡፡ ይህ አንድነት ደግሞ በአንድ ጀምበር የተገነባም አይደለም፡፡ ለዘመናት ሲገነባ የኖረ ነው፡፡ በሆነ አጋጣሚና በሆነ ግርግር ላይ ሊፈርስ የሚችል አይደለም ፡፡
ነገር ግን የኢትዮጵያን አንድነት የሚጎዳው ብሄራዊ አንድነት ነው ወይስ ምንድነው አንድነትን ሊጎዱ የሚችሉት? የሚለውን ነገር ካየን የኢትዮጵያን አንድነት ሊጎዳ የሚችለው ነገር ፍትህ ሲጠፋ ነው፡፡ አንዱ ቤተኛ አንዱ ባይተዋር ተደርጎ የሚሰደድበት ስርዓት እዚች አገር ውስጥ ካለ ኢትዮጵያዊነት በቀላሉ ይፈርሳል ባንልም ግን ሊሸረሸርና ሊጎዳ ይችላል፡፡ በኢትዮጵያዊያኖች መካከል እኩል ተጠቃሚነት ከሌለ ኢትዮጵያዊነት ሊጎዳ ይችላል፡፡ በእኔ ግምገማና በሁላችንም እይታ ኢትዮጵያዊነትን ሊጎዱ የሚችሉ በሽታዎችና ነቀርሳዎች እነዚህ ናቸው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ከዚህ በስተቀር የኢትዮጵያን አንድነት ሊጎዳ የሚችል ምንም ነገር የለም፡፡ እንዲያውም የኢትዮጵያን አንድነት ለማጠናከር ብሄር ብሄረሰቦችንም ብሄራዊ ማንነታቸውን እንዲያጠናክሩ ማድረግ አንድ ጉዳይ ሆኖ በዚህ ፌዴራላዊ አወቃቀር ሁሉም ክልል በየብሄራዊ ማንነቱ ለየአካባቢው ሲሰራ፤ ለየአካባቢው፣ ለየክልሉ መስራቱ አንድ ጉዳይ ሆኖ አገራዊ እይታ ሊኖረው ግን ይገባል፡፡ ሁልጊዜ በየቤታችን የራሳችንን ጉዳይ ስንሰራ አገራዊ እይታ ቢኖረን በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ ክልል ወይም አንድ ብሄር በራሱ ብቻ በሚሰራው ዘላቂ ጥቅሙ ሊረጋገጥለት አይችልም፤ ዘላቂ ሰላሙ ሊረጋገጥለት አይችልም፤ ዘላቂ እድገት ሊመጣለት አይችልም፡፡ እድገት ሊመጣ የሚችለው በጋራ ስንሆን ነው፡፡
በአገራችን ላይ ዘላቂ ለውጥ በማናችንም ብሄር ብሄረሰቦች ሊመጣ የሚችለው በአንድነታችንና በህብረታችን ውስጥ እስከሆነ ድረስ ሁልጊዜ በየብሄራችን ማንነታችንን ለማጠናከርና ለማጎልበት የምንሰራውን ያህል ሁሉ ለአገራዊ አንድነታችንም ሁልጊዜ እያሰብን እንደ አንድ ትልቅ ስራ ወስደን መስራቱ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ነው የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ዘላቂ ጥቅማችን ሊከበርና ሊጠበቅ የሚችለው፡፡ ስለዚህ ወደፊትም ከዚህ በበለጠ አሁንም እየተጀመረ ባለው ህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች በልማቱም በኢኮኖሚውም ለውጥ ማምጣት በዚያ ላይ ተግቶ መስራቱ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱንም ማጠናከር ማጎልበት እጅግ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ አሁንም እየተጀመሩ ያሉትን ጉዳዮችና ሌሎች አዳዲስ አንድነታችንን ይበልጥ እያጠናከሩ የሚሄዱ ጉዳዮችን በማጎልበትና በማጠናከር ይገባል፡፡ ይበልጥ እንድነታችንን ለማጠናከር እንደ አንድ ትልቅ ስራ መስራቱ አስፈላጊና ዘላቂ ጥቅማችንን ሊያስጠብቅልን የሚችል ነው፡፡
ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው ፌዴራሊዝም ብዝሀነታችንን ለማስተናገድ ተብሎ የተነደፈ ስርአት ነው፡፡ ይህ ህዝብን ለመበተን አይደለም፡፡ እኩልነትን በማረጋገጥ አንድነትን ለማምጣት ነው፡፡ የፌዴራሊዝም ዋና ዓላማው በብዝሀነትና ብሄር ላይ የተመሰረተ አንድነት ማምጣት ነው፡፡ ስለዚህ ብሄራዊ ማንነት ለአንድነት መሰረት ነው፡፡ ተቃርኖ ሊኖረው አይችልም፡፡ መሰረት የሌለው ቤት ቤት ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ የእኛ አገር አንድነቱ መሰረቱ ብሄር ነው፡፡ እነዚህ ያሉ እውነታዎች ናቸው፡፡ መሰረቱ ከተዳከመ አንድነት የሚባል ነገር ይፈርሳል፡፡ የእኛ ጠንካራ መሰረት ጠንካራ ብሄራዊ ማንነታችን ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህ ሲባል መብቶቹ በትክክል መረጋገጥ አለባቸው፡፡ የተሟሉ መብቶች መኖር አለባቸው፡፡ የዴሞክራሲ መብቶችም ሆኑ የልማት መብቶች፣ በተለያየ መልኩ የሚገለጸው ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ብሄራዊ ማንነታችን ለአንድነት መሰረት ነው፡፡
የአገራዊ ማንነትን ማዳከም የሚባለውን በተጨባጭነት ብናየው፤ በአንድነት በኩል በተጨባጭ አገራችን ተዳክሟል ማለት አንችልም፡፡ የተጠናከረ አንድነት ነው ያለን፡፡ ስርአትን ከስርአት ማነጻጸር አስፈላጊ ባይሆንም ካለፈው ስርአት አነጻጽረን ስናየው ህዝቦች መብታቸው በጣም በተረጋገጠበት፤ የእኩልነት መብቶቻቸው በቋንቋ፣ በባህልና በታሪክም ተከባብረው የማይተዋወቁ ህዝቦች እየተዋወቁ ነው የሄዱት፡፡ ከጫፍ ጫፍ ብዙ ነገር ነው እየተማርን ያለነው፡፡ አገራችንን እያወቅን ነው ያለነው፡፡ በልዩነቱ አንድነቱ ነው እየተገነባ ያለው፡፡ በፊት ልዩነቱም አይታይም፡፡ የተደፈነ፣ የተዘጋ ነበር፡፡ ግን የሚያስተሳስረን ታሪክ ስለነበረን በታሪካችን ነው የቆየነው፡፡ ብዙ ውጣ ውረድ ያለፈ ህዝብ ስለሆነ፡፡ ለሺህ ዘመናት እየተባለ የሚገለጸው ብዙ ታሪክ አለው፡፡ ብዙ መጥፎና በጎ ነገር ያለፈ ስለሆነ አንድነቱን ጠብቋል፡፡ ግን የተሟሉ መብቶች ተረጋግጠዋል ማለት አይቻልም፡፡ ጥቅሞች ተረጋግጠዋል ማለት አይቻልም፡፡ በጭቆናም በችግርም ሆኖ አንድነቱን የጠበቀ ነው፡፡ በዚህ ስርአት ጭቆናውን እየፈታነው የጎደለውን ነገር እየሞላን ነው ያለነው፡፡ የበለጠ አንድነቱን እንዲያጠናክር እንጂ ታሪኩን ለማጥፋት አይደለም፡፡ በታሪክ ላይ ነው ሌላ ታሪክ እየተገነባ ያለው፡፡ ስለዚህ ፌዴራሊዝም የብሄራዊ ማንነት መሰረቱ ስለሆነ አንድነትን የበለጠ ለማጠናከር የሚጠቅም ነው፡፡ አንዳንድ የሚታዩ ችግሮችም ካሉ ምንጫቸው እሱ አይደለም፡፡ ብሄራዊ አንድነት ስለተከበረ አይደለም፡፡ የጋራ የሚያደርጉን እሴቶችን መማር አለብን፡፡
ህዝባችን ብዙ ውጣ ውረድ አልፏል። ነጻነቱን ለምን ጠበቀ? ከስንት ጠላት ተፋልሞ ነው ይህን አገር የጠበቀው። የእገሌ ብሔር የእገሌ ብሔር ተብሎ እየተበታተነ አይደለም። ሲበታተን ቀዳዳ ለጠላት የሰጠ የተጋለጠበት፤ ሲተባበር ደግሞ አገሩን ጠብቆ የሄደበት ብዙ የጋራ የሁላችን ታሪክ አለ። ይህ የጋራ ነው።
ከታሪኮቻችን መማር አለብን። የጎደሉን ነገሮች አሉ፤ አንድነታችንን የበለጠ ማጠናከር እንጂ ብሔራዊ ማንነት አይደለም ችግሩ። እሱ የተለየ አጽንኦት ስለተሰጠው አይደለም። እሱማ መረጋገጥ አለበት ነው ያልነው፤ የጎደለ ነገር ነው የሞላው በዚህ ስርዓት። ይህ የጥንካሬያችን ምንጭ ነው። ተደጋግሞ እንደሚገለጸው በልዩነታችን የመጣ አንድነት ነው ያለው። እንጂ ልዩነት አጥፍተን፤ የብሔር ማንነት አቀዛቅዘን አንድነት የሚባል ነገር ልናመጣ አንችልም። አንድነቱ የሚፈርስ ነው የሚሆነው። ከጋራ እሴቶቻችን ግን ሁላችን መማር አለብን ነው ያልነው። የኢህአዴግ ስብሰባም ሳይቀር ወጣቱ ብቻ ሳይሆን ሁላችን እንማር ነው ያልነው። ያለፉ የሕዝቦች ታሪኮቻችን አሉ። አንድነቱን ለማጠናከር የጎደለ ነገር ግን አለ። ብሔራዊ ማንነቱን የመቀነስ ሳይሆን የጎደለውን መሙላት አለብን። ብዙ የጎደሉ አሉ፥ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ ብዙ ድህነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሉ። በጥቅማጥቅም ብዙ ድሆች አሉ። ያልተጠቀመ ከሆነ ችግር ነው ማለት ነው። ለሌላ ግጭት መንስኤ ነው የሚሆነው። ስለዚህ ለግጭት መንስኤ የሆኑትን በሙሉ ለመቀነስ ጥረት ማድረግ አለብን፤ የበለጠ ጠንካራ አንድነት እንዲኖረን።
በሌላ በኩል የጋራ እሴቶችን ሁላችን ማወቅ አለብን። እዚህ ላይ የጎደለ ነገር አለ። ሚዛኑ የተዛባ መስሎ የሚታየውም ለዚህ ነው። ብሔራዊ ማንነቱን አዳክመን እሱ ስለተጠናከረ የመቀነሰ ሳይሆን የጎደለችው በአመለካከትም አንድ ቤት ነው እየሠራን ያለነው። የጋራ ፕሮጀክት ተብሎ በተለያየ መልክ የሚገለጽ ነው። ለዚህም ተመሳሳይ አረዳድ እንዲኖረን ሁሉም ድርሻ ያለው ነው፤ ሁሉም ቤተኛ ነው። ስለዚህ የየራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት። አስተሳሰባችን ራዕያችን፤ አሁን መካከለኛ ገቢ እያልን የምንቀሳቀሰው እንደ አገር ነው። እንደ ህዝብ መለወጥ ነው የምንፈልገው። በዚህ ላይ በየክልሉ ታጥሮ ሳይሆን አገር አቀፍ እይታዎችን የመያዝ፣ ተደጋግፎ የመልማት፤ በመሰረተ ልማት ተሳስረናል፤ በመንገድ፣ በኤሌክትሪክና በመሳሰለው። ይህ መጠናከር አለበት፤ የበለጠ ትስስሮቻችን አንድነታችን በጣም ያጠናከራል። እዚህ የጎደሉትን እንሙላ፤ ያልተጠቀመ ህዝብ እንዲጠቀም ማድረግ አለብን።
ስለዚህ አንድነታችን ለማጠናከር በኢኮኖሚው ዘርፍ የሚሠሩ ብዙ ሥራዎች አሉ ማለት ነው። በገበያ የምናስተሳስረው፤ በየክልል ታጥሮ አይደለም እድገትና ልማት የሚመጣው። በየአካባቢው መልማት የሚችለውን ያህል እናለማለን፤ ይህ ግን እስፔሻላይዜሽን የምንለው ነው። በየአካባቢው የተለያየ ምርት እና የምንተሳሰርበት ገበያ፤ ሁሉም በአንድ አካባቢ እንዲመረት አይደለም። በገበያም ትስስር አንዱ ጋር የጎደለውን አንዱ የሚሞላበት። ተደጋግፈን፤ በገበያም ተሳስረን፥ በኢኮኖሚ ተጠቃሚነታችን ከፍ የምናደርግበት ነው። አንድነታችንን ለማጠናከር መወሰድ ያለባቸው ተጨማሪ እርምጃዎች አሉ ነው እያልን ያለነው። እንጂ ብሔራዊ ማንነት ላይ ያልሆነ ሥራ ተሠርቷልና እንቀንሰው አይደለም። ያቺ የጎደለችዋን አሟልተን የበለጠ አንድነታችንን የሚያጠናክር ሥራ መሥራት ይቻላል። ለአንድነቱ ብሎ ብቻ ሳይሆን ለበለጠ ተጠቃሚነትና የበለጠ ለማድረግ እንድንችል ነው። ጠንካራ ከሆንን በሁሉም ለጠላትም ሳይቀር የሚያስፈራ ነው የምንሆነው። ለምን ትልቅ ጉልበትና አቅም አለን። ማንም የሚደፍረው አገር አይሆንም። ሁለት ሶስቴ አስቦ ነው የሚመጣው። ለውጭ ጠላትም ሳይቀር ነው አንድነታችን የሚያስፈልገው።
ዋናው ግን ለራሳችን ተጠቃሚነት፣ ልማት፣ እድገት፣ የህዳሴ ጉዞ ለማፋጠን የግድ በአንድነት ዙሪያ የጎደሉንን፥ ከአመለካከት ጀምሮ በኢኮኖሚም በመሰረተ ልማትም፥ እና የባህል ልውውጥ፥ ሕዝብ ለህዝብ በሚል የተጀመረውም ተጠናክሮ ነው መሄድ አለበት። በሙዚቃና በዘፈን ብቻ አይደለም የተለያዩ አካባቢዎች መስማት ያለብን። ሕዝብ ለሕዝብ ማገናኘት አለብን። ምሁር ለምሁር መገናኘት አለበት። ወጣት ለወጣት መገናኘት አለበት። የበለጠ መተሳሰር አለብን እንጂ ወደ የክልል አጥር አይደለም መግባት ያለብን፥ ያ መፍረስ ነው ያለበት ። አጥር መኖር የለበትም፥ አስተዳደራዊ ቅርጽ ነው። ዋናው ይዘቱ ግን ትስስሩ ነው።
ያ መልክ ነው። ይዘቱ እንዳልነው ነው፥ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩ ሄደን ሄደን አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ እንፍጠር ያልነው ዋናው ጉዳይ። ይህን ለማጠናከር እንሥራ በሚል ነው ውይይት የተካሄደው።

 በጋዜጣው ሪፖርተሮች 

Published in ፖለቲካ

ስደተኞችንና ተቀባዮችን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ፕሮጀክት በስደተኛ ጣቢያዎች ተግባራዊ እየተደረገ ነው፤

በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን፣ በሶማሊያ፣ በሱዳንና በኤርትራ ባለው ሰላም መደፍረስና የተለያዩ ችግሮች ሳቢያ ነፍሴ አውጪኝ ብለው አካባቢያቸው ለቀው ድንበር ተሻግረው የመጡትን ከ800ሺ በላይ ስደተኞች ተቀብላ እያስተናገደች ትገኛለች፡፡ ስደተኞቹ በሰፈሩባቸው አካባቢዎች ለቤት መስሪያና ለማገዶ በአገሪቱ ደን ሀብት ላይ ጉዳት ያደርሳሉ፡፡ የተለያዩ አገልግሎትን የሚሰጡ መሰረተ ልማቶችን ከነዋሪው ጋር ስለሚጋሩ ጫና መፍጠራቸው አልቀረም፡፡
ይህን ለመቋቋም ስደተኞችን ተቀብለው በሚያስተ ናግዱ የአገሪቱ ክልሎች የሚተገበር ፕሮጀክት ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ፕሮጀክቱ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚደርሰውን ጫና ማቃለልን ዓላማው አድርጓል፡፡ ከዓለም ባንክ በተገኘ 100 ሚሊዮን ዶላር የሚተገበረው የስደተኞች ተፅእኖ ምላሽ ልማት መርሃ ግብር በጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሶማሌ ፣አፋርና ትግራይ ክልሎች እየተተገበረ መሆኑን በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የስደተኞች ተፅእኖ ምላሽ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ንጋቱ ቦጋለ ይናገራሉ፡፡
በ16 ወረዳዎች 116 ቀበሌዎች ላይ እየተተገበረ ባለው ፕሮጀክት አንድ ሚሊዮን 171 ሺ868 ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አስተባባሪው ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ 534ሺ 960ዎቹ ስደተኛ ተቀባይ የአካባቢው ነዋሪዎች ናቸው፡፡
እንደ አቶ ንጋቱ ገለጻ የስደተኞች ተጽእኖ ምላሽ ልማት ፕሮጀክት በ2009 ዓ.ም ወደ ትግበራ የገባ ሲሆን ፕሮጀክቱ አራት ክፍሎች አሉት። በአንደኛው ክፍል እንደ ትምህርት፣ጤና፣ ውሃና መንገድ ያሉ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት የሚገነቡ ይሆናል፡፡ ይህም ስደተኞችንም ሆነ ከስደተኞች ውጭ ያሉ ነዎሪዎችን በዘለቄታዊነት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲኖራቸው በማድረግ ህይወታቸውን እንዲለውጡ ያግዛል። ሁለተኛው ክፍል በተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤና ልማት ላይ በመስራት ከስደተኞች ጋር ተያይዞ የሚመጣው የመሬት መራቆትና የደን መመናመን ችግሮች መፈታትን ትኩረቱ አድርጓል፡፡
ሶስተኛው በግብርናና በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ ለአካባቢው ህብረተሰብ ድጋፍ ይሰጣል፡፡ ይህም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይረዳል፡፡ አራተኛው ለአካባቢው ሰዎች የስራ ዕድሎች በመፍጠር የተሻለ ገቢ እንዲኖራቸው ያስችላል። ይህም በአካባቢው ህብረተሰብና በስደተኞች መካከል በተፈጥሮ ሀብት ሽሚያ ሳቢያ ሊከሰት የሚችለውን ግጭት መከላከል ይቻላል። በስደተኞችና በነዋሪዎች መካካል ጠንካራ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲፈጠር ያደርጋል ባይ ናቸው።
በዓለም ባንክ ድጋፍ እየተተገበረ የሚገኘው ፕሮጀክት በሂደት የተጠቃሚዎች ቁጥርም እንዲጨምር ይደረጋል ያላሉ-አቶ ንጋቱ፡፡ በ2010 በጀት ዓመትም ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ 596 ሚሊዮን 427ሺ827 ብር ተመድቦ የተለያዩ የልማት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ነግረውናል፡፡
በምዕራፍ አንድ ከሚሰሩት የልማት ስራዎች መካካልም የትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ ጥገናና ማስፋፋት፤ የጤና ኬላ ግንባታ ፣የውሃ ተቋማትና መንገድ ስራ ይገኙበታል፡፡ በምዕራፍ ሁለት ደግሞ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራዎች፣ አነስተኛ የመስኖ ግንባታዎችና ሀይል ቆጣቢ ምድጃዎችን ለስደተኞቹ የማቅረብ ስራዎች ተካተውበታል፡፡
ሶስተኛው ምዕራፍ የሰብል ምርትና ምርታማትን መጨመር የሚያስችሉ ስራዎች የሚሰሩ መሆናቸው አስተባባሪው አስታውሰው ለስራ አጥ ወጣቶች የስራ ዕድል የመፍጠር ተግባር በአራተኛው ምዕራፍ የሚተገበር መሆኑን ገልጸውልናል፡፡
ፕሮጀክቱ ዘግይቷል ብለው የሚናገሩ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ አቶ ንጋቱ ‹‹ ፕሮጀክቱ ዘግይቷል ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ፕሮጀክቱ የጸደቀው በ2009 በጀት ዓመት ነው፡፡ ፋይናንሱ የተለቀቀው በዚሁ ዓመት ታህሳስ ወር ላይ ነው፡፡ ከዚህ ወር ጀምሮ የፕሮጀክት ማስተባባሪያ ክፍሎች በማደራጀት ወዲያው ወደ ስራ ተገብቷል›› ብለዋል፡፡ የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ ስደተኞች ወደ እነዚህ አካባቢዎች በመምጣታቸው እየደረሰ ያለውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ነው የሚሉት አስተባባሪው ለምሳሌ ስደተኞች ለማገዶና ለቤት መስሪያ እንጨት ይፈልጋሉ፡፡ በዚህ የተነሳ በአካባቢው የደን ጭፍጨፋ ስለሚኖር ደኑ ይራቆታል፡፡ የፕሮጀክቱ ዓላማም ይህን የተራቆተ አካባቢ በማልማት መልሶ እንዲያገግም ማድረግ ነው፡፡
ሌላው ስደተኞች ውሃ፣ትምህርትና የጤና አገልግሎቶችን ይፈልጋሉ፡፡ እነዚህን አገልግሎቶች በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችሉ በርካታ የልማት ስራዎች ይሰራሉ፡፡ ይህም በስደተኛውና በስደተኛ ተቀባይ ማህበረሰብ መካካል ያለውን መስተጋብር ያጠናክራል፡፡ በአካባቢው የሚታዩ የልማት ክፍተቶችን ጭምር ይሞላል፡፡ እናም ፕሮጀክቱ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ የፕሮጀክቱን ጠቀሜታ ያስረዳሉ፡፡
ፕሮጀክቱ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ዓመታት የሚቆይ መሆኑን የሚናገሩት አስተባባሪው አባዛኛዎቹ ግንባታዎች የሚሰሩት በቀበሌ ደረጃ በመሆኑ ለአንድ ፕሮጀክት ከሚወጣ አጠቃላይ ወጪ 15 በመቶ በማህበረሰቡ በጉልበትና በገንዘብ ይሸፈናል፡፡ እናም አሉ አቶ ንጋቱ ዘንድሮ ከተያዘው ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ብር ውስጥ 34 ሚሊዮኑ በማህበረሰቡ የሚሸፈን ይሆናል፡፡ ዘንድሮ ከህብረተሰቡ በጥሬ ገንዘብ ይሰበሳባል ተብሎ ከታቀደው 11 ሚሊዮን ብር በአሁኑ ወቅት 10 ሚሊዮን ብር ማሰባሳብ ተችሏል፡፡
በአጠቃላይ በተያዘው በጀት ዓመትም በአምስቱም ክልሎች 336 ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማቶች የሚገነቡ ሲሆን በአምስቱ ክልሎች የሚገኙ 24 የስደተኛ መጠለያ ካምፖች የመሰረተ ልማት አውታሮች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
‹‹እስካሁን ድረስ ከፕሮጀክቱ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ያጋጠመን ችግር የለም፡፡ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየተሰራ ይገኛል፡፡ በአካባቢዎቹ የደረሰውን አሉታዊ ተጽእኖ በአምስት አመት ውስጥ ስለማይፈታ ይራዘማል የሚል እምነት አለኝ›› ሲሉም ተደምጧል፡፡
የሱማሌ ክልል 192ሺ ስደተኞችን ያህል ተቀብሎ እያስተናገደ ይገኛል። ይህን ተከትሎም የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ባሉባቸው የክልሉ አካባቢዎች በሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫናዎች እንደሚደርስባቸው በክልሉ ግብርና ቢሮ የስደተኞች ተጽእኖ ምላሽ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አምዴ መሀመድ ይናገራሉ፡፡ በፕሮጀክቱ አራት ወረዳዎች እንደሚካተቱ ገልጸው በመርሃ ግብሩ ልዩ ልዩ የልማት ስራዎችን እንደሚያከናወኑ ተናግረዋል፡፡ በተለይም ስደተኞችን ተቀብለው እያስተናገዱ የሚገኙ አካባቢዎችን ጫና በማቃለል ረገድ ትልቅ እፎይታን ይሰጣል ባይ ናቸው።
አቶ አምዴ እንዳሉት በክልሉ የጤና፣ የውሃና የትምህርት ተቋማት የተገነቡት ነዋሪዎችን ታሳቢ በማድረግ ነው። እንደ አጋጣሚ ሆኖ በርካታ የሶማሊያ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣታቸው ለአካባቢው ነዋሪዎች አገልግሎት የሚሰጡ የውሃ፣ የትምህርትና የጤና መሰረተ ልማቶችን ይጠቀማሉ፡፡ ይህም በአገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍና ላይ ጫና መፍጠሩ አልቀረም። ስለሆነም ፕሮጀክቱ ይህን ችግር በማቃለል ረገድ ትልቅ ሚና አለው፡፡
የጋምቤላ ክልል 400 ሺ የሚጠጉ ስደተኞችን ተቀብሎ እያስተናገደ እንደሚገኝ የሚገልፁት ደግሞ የክልሉ የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሎው አቡኘ ናቸው፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች እንዲደር ስባቸው እያደረገ ነው፡፡ መርሃ ግብሩ ሁሉንም ችግሮች ሙሉ በሙሉ ይፈታል ባይባልም በተወሰነ ደረጃ ለጫናዎቹ መፍትሄ ይሰጣል ይላሉ።
በተያዘው በጀት ዓመት በክልሉ ባሉ አምስት የስደተኛ ጣቢያዎች የሚገኙ 37ሺ 950 የአካባቢውን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ የልማት ስራዎች እንደሚከናወኑ ዶክተር ሎው ገልፀዋል፡፡ የትምህርትና ጤና ተቋማትን ለመገንባትና ለመጠገን ሥራው በጨረታ ሂደት ላይ ይገኛል፡፡ የውሃ ተቋማትን ለመገንባት የምርመራ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ ከ50 በላይ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ይሆናሉ ብለዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ በክልሉ ስደተኛ ጣቢያዎች አካባቢ ለሚገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች 100 ሚሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ 30 ሚሊዮን ብር ተለቆላቸዋል፡፡
እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለፃ በደቡብ ሱዳን በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት ስደተኞች በብዛት ወደ ጋምቤላ እየፈለሱ ናቸው። በየዓመቱም እየጨመረ ነው፡፡ እነዚህም በአምስት የተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ሰፍረዋል፡፡ የጋምቤላ ክልል ለብዙ ዓመታት ስደተኞችን ተቀብሎ እያስተናገደ ይገኛል፡፡ ስደተኞች በተወሰኑ አካባቢዎች በሚገኙ የመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ተሰባስበው ስለሚቆዩ በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚደርሰው ውድመት ከፍተኛ ነው፡፡
አሉታዊ ተፅዕኖው ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ ቀጣይነት ያለው መሆኑም ችግሩን አሳሳቢ እንዳደረገው ዶክተር ሎው ገልፀዋል፡፡ በማህበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ላይም ተፅዕኖው የጎላ ነው፡፡ እናም ፕሮጀክቱ በስደተኞች የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጌትነት ምህረቴ

Published in ኢኮኖሚ

ሰሜን ኮሪያ ከደቡብ ኮሪያ ጋር ለመወያየት ፈቃደኝነቷን አሳይታለች

በዋሽንግተን ‹‹የፕላኔታችን ክፉ ጠላት››፣ በጃፓንና ደቡብ ኮርያ ደግሞ ‹‹ሁሌም ለፀብ አጫሪነት የምትተጋ›› የሚለውን ካባ የተጎናፀፈችው ሰሜን ኮሪያ አሁንም በአወዛጋቢ ድርጊቷ ገፍታበታለች፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ማዕቀቦች ቢጣልባትም ከእርምጃዋ ሊገታት አልቻለም፡፡
‹‹ባላንጣዬ›› ከምትላት አሜሪካ የሚሰነዘርባትን ዛቻና ማስፈራሪያ ‹‹ፋይዳ ቢሶች›› በማለት ለዋሽንግተን እንደማታንስ የምትገልፀው ፒዮንግያንግ የሚሳኤል ሙከራና የኒውክሌር ፕሮግራሟን ገፍታበታለች፡፡ ‹‹ራስን ለመከላከል የሚተገበር›› በሚል አቋም፡፡
ሲ ኤፍ አር የተሰኘ የሀሳብ አመንጪ ምሁራንን አስተያየት በድረገፅ የሚለቅ ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ያደረገ ተቋም ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው ፒዮንግያንግ ማንንም ባለመፍራት የምትፈልገውን እርምጃ መውሰዱን ተያይዛዋለች፡፡ ከፈረንጆቹ ሚሊኒየም በኋላ እንኳን ባደረገቻቸው የኒውክሌርና የሚሳኤል ሙከራዎች በመንግስታቱ ድርጅት ዘጠኝ ያህል ማዕቀቦች ተጥለውበታል፡፡ ፒዮንግያንግን የሚያስደነግጡና ከድርጊቷ እንድትታቀብ ባያደርጉም፡፡
እንደውም ወጣቱ መሪ ኪም ዮንግ ኡን ‹‹ማዕቀቦቹ ቢያጠናክሩን እንጂ የሚያስፈሩን አይደሉም››በማለት መናገራቸውን ቢቢሲ በዘገባው አመልክቷል፡፡ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ‹‹ሰሜን ኮሪያ ከፀብ አጫሪነት ድርጊቷ የማትታቀብ ከሆነ ድራሿን ነው የምናጠፋው›› በማለት ዝተዋል፡፡
የሁለቱ መሪዎች የቃላት ጦርነት አሁንም እንደከረረ ቀጥሏል፡፡ በቅርቡ ኪም ዮንግ ኡን አዲስ ዓመትን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት ‹‹የኒውክሌር ቁልፉ ጠረጴዛዬ ላይ ነው›› በማለት አሜሪካንን ለማውደም የሚችል የኒውክሌር ቴክኖሎጂ መታጠቃቸውን ገልፀዋል፡፡ ይህን ተከትሎም ፕሬዚዳንት ትራምፕ ፒዮንግያንግ ምንም ብትወራጭ ከአሜሪካ አታመልጥም ዓይነት መልዕክታቸውን ‹‹ የእኔ ቁልፍ ካንተ ይበልጣል›› በማለት የበላይ ነታቸውን ለማሳየት ሞክረዋል ይላል ሮይተርስ፡፡
ፒዮንግያንግ ለአሜሪካ ማስጠንቀቂያ መስጠትን ያለሙ ናቸው ያለቻቸውን የተለያዩ መካከለኛ፣ ረጅምና አህጉር ተሻጋሪ ሚሳኤሎችን የማስወንጨፍ ሙከራዎችን አድርጋለች፡፡ ለቃላት ጦርነቱ እጅ መስጠትን የማይወዱት ፕሬዚዳንት ትራምፕ የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ሶስተኛው የዓለም ጦርነት እንዳይነሳ ጠንከር ያለ ማዕቀብ በፒዮንግያግ ላይ እንዲጥል በፅኑ ሲያሳስቡ ከርመዋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ኒኪ ሃሌይ ‹‹የድርድር ጊዜ አብቅቷል፤ አሁን ጊዜው ተግባራዊ እርምጃ የሚወሰድበት ነው›› በማለት የፕሬዚዳንት ትራምፕን አቋም አንፀባርቀ ዋል፡፡ለዚህ ደግሞ ጠንካራ ማዕቀቦች እንዲጣሉ ከማድረግ ጀምሮ አገሪቱን በመገሰፅና በመተቸት የምክር ቤቱ አባል አገራት ፅኑ አቋም ሊኖራቸው እንደሚገባ ማሳሰባቸውን የሮይተርስ ዘገባ ያትታል፡፡
ፒዮንግያንግ ላይ ጠንካራ እርምጃ በመውሰድ ረገድ ሩስያና ቻይና ለዘብተኛ አቋም መያዛቸውን በመግለፅ አሜሪካ አገራቱን ትተቻለች፡፡ ሩስያና ቻይና በበኩላቸው ‹‹ከወታደራዊ እርምጃ በፊት የክብ ጠረጴዛ ውይይት ይቀድማል›› ይላሉ፡፡ በአሜሪካ የሚሰነዘርባቸው ትችትም ተገቢነት የሌለውና ውሃ የማይቋጥር እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡
ፒዮንግያንግ በፈረንጆቹ 1985 የኒውክሌር ልማትን በመቀነስ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን ለማዳከም በመንግስታቱ ድርጅት የወጣውን ስምምነት ብታፀድቅም ይህ ግን ከስምንት ዓመት በላይ ሊጓዝ አልቻለም፡፡ በፈረንጆቹ 2003 ከስምምነቱ መውጣቷን ሰሜን ኮርያ አስታወቀች፡፡ በሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ልማት ዙርያ ጥናት የሚያካሂዱት ሚስተር ስኮት ስናይደር ስምምነቱ ለሰሜን ኮሪያ የሚጠቅማት ሆኖ ባለማግኘቷ ልታቆመው መቻሏን ይናገራሉ፡፡
ምክንያቱም የኒውክሌር ልማት ለህልውናዋ ወሳኝና አስፈላጊ መሆኑን ሰሜን ኮሪያ በፅኑ ታምንበታለች ይላሉ፡፡ ሌሎች የዘርፉ ምሁራንም ፒዮንግያንግ ከአሜሪካ ለሚሰነዘርባት ዛቻ የኒውክሌር ልማትን በማስፈራሪያነት ስለምትጠቀም ስምምነቱን ወደ ጎን መተዋ ብዙም አይደንቅም ባይ ናቸው፡፡
ከስምምነቱ መውጣቷን ካወጀች ከሶስት ዓመት ቆይታ በኋላ የመጀመሪያውን የኒውክሌር ሙከራ በማድረግ እወቁልኝ አለች፡፡ የፀጥታው ምክር ቤትም ላልተገባው ድርጊቷ የጦር መሳሪያ አቅርቦት፣ ለሚሳኤል ልማት የሚውሉ ግብዓቶችና በተመረጡ የቅንጦት ሸቀጦች ላይ ማዕቀብ በመጣል ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ ከለከለ፡፡
የኒውክሌር ልማቷን ለመዝጋት መወሰኗን ለቻይና በማሳወቅ የዮንግቢዮን ኒውክሌር ማብላያ ጣቢያን መዝጋቷን ገለፀች፡፡ በፈረንጆቹ 2008 እንዲህ ብትልም በዓመቱ ሁለተኛውን የኒውክሌር ሙከራ አደረገች፡፡ የመንግስታቱ ድርጅትም ለዚህ አፀፋ የሚሆን ተጨማሪ ማዕቀብ ጣለባት፡፡ ይህም ቢሆን ግን የፒዮንግያንግን እርምጃ የሚገታ አልሆነም፡፡
ሰሜን ኮሪያን ለ17 ዓመታት የመሩትን ኪም ዮን ኢል ሞትን ተከትሎ ወደ ሥልጣን የመጡት ልጃቸው ኪም ዮንግ ኡን አገራቸውን የማዕቀብ ጎተራ ሲያደርጓት ተስተውሏል፡፡ በርካቶች ‹‹ትዕቢታቸው ከዕድሜያቸው በላይ›› እንደሆነ የሚናገሩላቸው ወጣቱ መሪ በተከታታይ የተለያዩ የሚሳኤል ሙከራዎችን በማድረግ ‹‹ጠላታችን›› ለሚሏት አሜሪካና አጋሮቿ ማንነታቸውን ለማሳየት ሞክረዋል፡፡
ወጣቱ መሪ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ እንኳ ከሰባት የማያንሱ የሚሳኤል ሙከራዎችን ማድረጋቸውን የፀጥታው ምክር ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡ እነዚህን ሙከራዎች ተከትሎም የጸጥታው ምክር ቤት የሰሜን ኮሪያ መሪና የተወሰኑ ባለስልጣናት ሃብት እንዳይንቀሳቀስ፣ የማዕድን ምርትን በተለይም የድንጋይ ከሰል እንዳታቀርብ፣ የነዳጅ ምርትን ወደ አገር ውስጥ እንዳታስገባ የሚከለክሉ ማዕቀቦች ጣለባት፡፡ የግብርና ምርቶች፣የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች፣ እንጨት፣ የባህር ምግቦችን ለውጭ ገበያ የምታቀርብበትን ዕድል የሚዘጉ ክልከላዎችንም አስተላለፈባት፡፡ ዜጎቿ በተለያዩ አገራት እንዳይሰሩ የይለፍ ፈቃድ (ቪዛ) እንዳያገኙ የሚያደርግና ሌሎች ማዕቀቦችንም አከናነባት፡፡
ማዕቀቦቹ ፒዮንግያንግን ከድርጊቷ ባለማስቆ ማቸው ሁሌም የምትብከነከው አሜሪካ በሰሜን ሶርያ ጉዳይ አጋሮቼ ከምትላቸው ደቡብ ኮሪያና ጃፓን ጋር ጥብቅ ቁርኝት በመፍጠር ስትንቀሳቀስ ቆይታለች፣ እየተንቀሳቀሰችም ይገኛል፡፡
በጃፓን አርባ ሺህ የሚጠጉ ፣በደቡብ ኮሪያ ደግሞ ከ28 ሺህ በላይ ወታደሮችን አሜሪካ ማሰማራቷን የኒውስ ስታር ድረ ገፅ መረጃ ያስረዳል፡፡ በተለይም የፒዮንግያንግ የቅርብ ጎረቤት ከሆነችው ደቡብ ኮሪያ ጋር ወታደራዊ ልምምድ እያደረገች ይገኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ደቡብ ኮሪያን ከሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ጥቃት ለመታደግ ፀረ ሚሳኤል መከላከያ ጋሻ (ታድ) ገንብታለች፡፡
በፒዮንግያንግ ጉዳይ መሃል ሰፋሪ የምትላቸው ሩስያና ቻይና የአሜሪካን ምክረ ሀሳብ በመደገፍ ሰሜን ኮሪያን ከዕኩይ ድርጊትዋ ለመግታት ከጎንዋ እንዲሰለፉ ተግታለች፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን ቻይናና ሩስያ በሚፈለገው ደረጃ እየተባበሩ አይደለም እስከ ማለት ደርሰዋል፡፡ ከሩስያና ቻይና የምትፈልገውን ያህል ድጋፍ ባታገኝም፡፡
ኪም ዮንግ ኡን ሰሞኑን ባስተላለፉት መልዕክት ለ34ኛው የልደት በዓላቸው አህጉር ተሻጋሪ የባላስቲክ ሚሳኤል ሙከራ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ ይህ የወጣቱ መሪ ንግግር ለአሜሪካው አቻቸው ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ባለፈ አገራቸው በኒውክሌር ልማት መርሃ ግብሯ ተጠምዳ እንዳለችና ለመንግስታቱ ድርጅት ማዕቀቦች የመገዛት ፍላጎት እንደሌላት ማሳያ ነው የሚሉ አሉ፡፡
ሰሞኑን በፒዮንግያንግና በዋሽንግተን መሪዎች መካከል ከተደረገው ‹‹የኒውክሌር ቁልፍ….››የቃላት ጦርነት በተቃራኒው በስጋት የተሞላውን የኮሪያን ባህረሰላጤ አየር ሊቀይር ይችላል የሚል ተስፋ የተጣለበት ዜና ከወደ ፒዮንግያንግ ተሰምቷል፡፡ ሰሜን ኮሪያ ከደቡብ ኮሪያ ጋር ለመወያየት ፍላጎት እንዳላት ገልፃለች፡፡ ይህም በሁለቱ አገራት መካከል በመሪዎች ደረጃ ውይይት ለማድረግ ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ የመጀመሪያው ነው ተብሏል፡፡
የመሪዎቹ ውይይት በውጥረት ለተሞላው የኮሪያ ባህረ ሠላጤ የመፍትሔ ጉዞ አንድ እርምጃ ወደ ፊት ተብሏል፡፡ ሌሎች በበኩላቸው የሰሜን ኮሪያ እርምጃ ለሠላም በር መክፈትን ያለመ ሳይሆን የኦሎምፒክ ውድድር ተሳትፎ ፍላጎቷን ለማሳካት ነው ይላሉ፡፡
ለዚህም አገሪቱ በደቡብ ኮሪያ በሚደረገው የኦሎምፒክ ውድድር ላይ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላት አስታውቃለች፡፡ የውይይቱ ሃሳብም የዚህ ስኬት መንደርደርያ ሳይሆን አይቀርም ባይ ናቸው፡፡ የሁለቱ አገራት የውይይት አጀንዳ የተለየ ይዘት እንዳለው አልጀዚራ መዘገቡን በአስረጅነት ያቀርባሉ፡፡
እንደ አልጀዚራ ዘገባ ሰሜን ኮሪያ ከወራት በኋላ በደቡብ ኮሪያ ፒዮንግቻንግ በሚደረገው የኦሎምፒክ ውድድር ተሳትፎዋን ትኩረቷን ታደርጋለች፡፡ ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ ጎረቤቷ የኒውክሌር ፕሮግራሟን ልታቆም በምትችለው አካሄድ ዙሪያ የመወያየት ፍላጎት አላት፡፡
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ሙን ጂ ኢን ውይይታቸው የሰሜን ኮሪያን የሚሳኤልና የኒውክሌር መርሀ ግብር አጀንዳው እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ ሰሜን ኮሪያ ግን ሙሉ ትኩረቷ የኦሎምፒኩ ውድድር ይሆናል ነው የተባለው፡፡ ይህም አጀንዳው እንደታሰበው ችግሮችን በመፍታት ዙሪያ ሊሆን ይችላል በሚለው ሃሳብ ላይ ውሃ ይቸልስበታል፡፡
የሰሜን ኮሪያ ዓለም ዓቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ተወካይ ቻንግ ኡንግ አገራቸው ከፈረንጆቹ የካቲት ዘጠኝ እስከ 25 በሚካሄደው የኦሎምፒክ ውድድር ላይ የመሳተፍ ፅኑ ፍላጎት እንዳላት መናገራቸውን የጃፓኑ የዜና ምንጭ ኮዮዶ ዘግቧል፡፡ ተወካዩ በውድድሩ ዙሪያ ለመምከር ወደ ሲዊዘርላንድ ማቅናታቸውም ነው የተመለከተው፡፡ እናም የሰሜን ኮሪያ የእንወያይ ጥያቄ ለሠላም ሳይሆን ለፒዮንግቻንግ ኦሎምፒክ ነው እየተባለ ነው፡፡ አገራቸው የተለያዩ የኦሎምፒክ ልዑካንን ወደ ደቡብ ኮሪያ ለመላክ መወሰኗም ተሰምቷል፡፡
በዮንግ ኡን አስተዳደር ውስጥ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ማይክል ማደን ሰሜን ኮሪያ በቀጣዮቹ ሶስት ወራት ውስጥ የሚሳኤል ሙከራ ልታደርግ ትችላለች የሚል እምነት እንዳላቸው መናገራቸውን ዴይሊ ስታር ድረ ገፅ ፅፏል፡፡ የፈረንጆቹ ወርሃ መጋቢት 2018 ከማለፉ በፊትም ‹‹አንድ የሚሳኤል ሙከራ እናያለን›› ብለዋል፡፡
ሰሜን ኮሪያ በደቡብ ኮሪያ የኦሎምፒክ ውድድር ላይ የመሳተፍ ፍላጎቷን ማንፀባረቋ ለሚሳኤል ማስወንጨፍ ዕቅዱ መራዘም ምክንያት ሳይሆን አልቀረም እየተባለ ነው፡፡ የኦሎምፒክ ውድድር ተሳትፎዋን ላለማጨለም በሚል ሰበብ ሙከራውን ሳታራዝም እንዳልቀረች የሚናገሩም በርካታ ናቸው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ እንደተባለው ፒዮንግያንግ ለሠላም ሳይሆን ለፒዮንግቻንግ ነው በሯን የከፈተችው ያስብላል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

Published in ዓለም አቀፍ

ኢህአዴግ ለ17 ቀናት በስብሰባ ላይ በነበረበት ወቅት በማህበራዊ ሚዲያው ብዙ ግምቶች ነበሩ፡፡ ከስብሰባው በኋላ ‹‹ምን ይባል ይሆን?›› ብለው በጉጉት የጠበቁ ብዙዎች ናቸው፡፡ ስብሰባው ተጠናቆ መግለጫ ተሰጠ፡፡ ከመግለጫው በኋላ ደግሞ ‹‹ምንም አዲስ ነገር የለውም›› የሚሉም አልጠፉም፡፡ ለመሆኑ አዲስ ነገር ምን ቢኖር ነበር? በመግለጫው ላይ አንድ ትልቅ ነገር አለ፡፡ በአገሪቱ ውስጥ እስካሁን ለተፈጠሩ ችግሮች ሁሉ ኢህአዴግ ‹‹ይቅርታ!›› ጠይቋል፡፡ በፖለቲካም፣ በባህልም፣ በሃይማኖትም ብንሄድ ከይቅርታ በላይ ምንም የለም፡፡ ዋናው ነገር ወደፊት እንዴት ይሁን? የሚለው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢህአዴግ በጥልቅ የታደሰውን ተግባር ላይ ማዋል አለበት፡፡
የአገሪቱ ሁኔታ ግን የመንግስት ኃላፊነት ብቻ አይደለም፡፡ የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ነው፡፡ ስለዚህ ሁላችንም በጥልቅ ልንታደስ ይገባል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር ግልጽ ነው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ለተፈጠሩ ችግሮች በውጭ አገር ሆነው ‹‹ለአገር ተቆርቋሪ ነን›› የሚሉ አክቲቪስቶች ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡ እኛ ደግሞ የእነርሱ አጀንዳ አስፈጻሚ ሆነናል፡፡ አሁን ባለው የአገሪቱ ሁኔታ እኛም እነርሱም ጥልቅ ተሃድሶ የምናደርግበት ነው፡፡ በነገራችን ላይ እነርሱ መለወጥ ካልቻሉ የእኛ መለወጥ ብቻ ለውጥ ያመጣል፡፡ አሁን መታደስ ያስፈለገን እኛ ነን፡፡ አንድ ‹‹የአገር ተቆርቋሪ ነኝ ባይ ›› አገር ሲያፈርስ አብረን እያፋረስነው ከሆነ መቼም ለውጥ ሊመጣ አይችልም፡፡ አሁን እኮ የሚቀለድበት ጊዜ አይደለም፡፡
ማንም በአገር ሙድ የሚይዝበት (የሚቀልድበት) ሁኔታ አይደለም፡፡ ይሄ በውጭ ሆኖ ‹‹በለው! ውቃው! ደብልቀው!›› የሚል አክቲቪስት ግን በአገር እየቀለደ ነው፡፡ እሱ አንተን አያይዞ ጭፈራ ቤት ‹‹አሸሸ ገዳሜ!›› ሲል ያድራል፡፡ ጋንጃና ሺሻውን እየማገ አገር ላይ ሙድ ይይዛል፡፡ በእነዚህ ‹‹አክቲቪስት›› ተብዬዎች የተጭበረበርን ይመስለኛል፡፡ የእነርሱ ዓላማ ኢህአዴግን ከሥልጣን ማውረድ ሳይሆን የዚህችን አገር ልማትና እድገት ከማይፈልጉ አካላት ጋር እየተወዳጁ አገር ማፍረስ ነው፡፡ የሚፈሰው እኮ የሰው ልጅ ደም ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ‹‹ኢህአዴግን በምን ትቃወሙታላችሁ?›› ቢባሉ ‹‹በብሄር ስለከፋፈለን›› ይላሉ፡፡ ይህን እያሉ ግን እያደረጉ ያሉት ‹‹እገሌ ብሄርን ውደድ፤ እገሌ ብሄርን አጥፋ›› ነው፡፡ እንዲህ ነው እንዴ ታዲያ የአገር ተቆርቋሪነት? እኛ እነርሱን መከተላችን ደግሞ ያሰቡት እንዲሳካላቸው አድርጓል፡፡ እነዚህን ሰዎች ዓላማቸውን እያሳካንላቸው ነው፡፡ መጀመሪያ ከመሬት ተነስተው ‹‹አምቦ ላይ ምድር ቀውጢ ሆናለች›› ይላሉ፡፡ በነጋታው ምድር ቀውጢ ይሆናል፡፡ ‹‹ይህን ያህል የአማራ ልጆች ተገደሉ፣ይህን ያህል የኦሮሞ ልጆች ተገደሉ›› ይላሉ፡፡ በሁለተኛውና ሦስተኛው ቀን እነርሱ ካሟረቱት በላይ የሰው ሕይወት ይጠፋል፡፡ ያንን ጥፋት ያደረሰው እዚሁ ያለ ሰው ነው፡፡ ያጠፋው የወገኑን ሕይወት ነው፤ ያወደመው የወገኑን ንብረት ነው፡፡ የገደልነው እኛ የሞትነውም እኛ ይሉሃል ይሄ ነው።
እዚህ ክልል ‹‹የመሰረተ ልማት ችግር አለ›› ይባላል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ያለውን ልማት አውድሙ ሲሉ ያዛሉ፤ ድብቁ አጀንዳቸው ያልገባቸው አፍላ ወጣቶቻችንም የታዘዙትን ያደርጋሉ። ይሄ ታዲያ በአገር መጫወት አይደለም? ወገኔ አትጭበርበር! ይሄ በውጭ ሆኖ ‹‹በዚህ ውጣ፣ በዚህ ውረድ፣ እገሌን አጥፋ…›› የሚልህ ከነቤተሰቦቹ አውሮፓና አሜሪካ ውስጥ ሆኖ ነው፡፡ የአንተ ወገን ደሙን ሲረጭ እሱ ውስኪውን ነው የሚረጭ፡፡ የአንተ ወገን በሀዘን ሲያለቅስ እሱ ዳንኪራውን ነው የሚጨፍር፡፡ ፌስቡክ ላይ ሻማ እያቀለጠ ፕሮፋይሉን ጥቁር በጥቁር ቢያደርግ እውነት እንዳይመስልህ፤ እዚህ ያለው ግርግር ጭሱም አይነካው፡፡ አገሪቱን ትርምስ ውስጥ የከተታት፣ ዩኒቨርሲቲዎችን እስከመዘጋት ያደረሳቸው ከውጭ ሆነው አክራሪ ብሄርተኝነትን የሚነዙ ሰዎች ናቸው፡፡ እሱ ከውጭ ሆኖ በፌስቡክ ‹‹የእገሌን ብሄር አስወጡ›› ይላል፡፡
በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ እነርሱን ሰምቶ በወገኑ ላይ ድንጋይ የሚወረውረው አሁን አሁን መብዛቱ ነው፡፡ አሁን ያለው የተማሪዎች ጥያቄ እኮ የትምህርት ጥራት ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ የብሄር እየሆነ ነው፡፡ እያሉ ያሉት ‹‹የአማራ ተማሪ ይውጣ፣ የትግራይ ተማሪ ይውጣ፣ የሶማሌ ተማሪ ይውጣ…›› ነው፡፡ እንዲህ ነው እንዴ ታዲያ የአገር ተረካቢ? አሁን መንቃት ያለበት ህዝብ ነው፡፡ ህዝብ አንድ ከሆነ ነው መንግስትንም ማስተካከል የሚቻለው፡፡ መንግስት መታደስ ባይችል እንኳን ህዝብ ከታደሰ የግድ መንግስትን ማንቃት ይችላል፡፡ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ህዝብ ጠንቅቆ ማወቅ አለበት፡፡ ከየት መጥታ የት እንደደረሰች ማጤን ግድ ይላል፡፡ የአገሪቱ ታሪክ የጦርነት ታሪክ ብቻ ሆኖ መቅረት የለበትም፡፡ እስከ መቼ ነው የበለጸጉ አገራት መሳለቂያ የምትሆነው? አንድ ነገር ልብ እንበል! እነዚህ ‹‹በለው! አጥፋው፣ አቃጥለው!..›› የሚሉ ሰዎች ዓላማ ምንድነው? እሺ ሥልጣን መያዝ ነው እንበል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ያለ መሰረተ ልማት ከወደመ፣ የሰው ልጅ ሕይወት ከጠፋ ምን አይነት አገር ነው የሚያስተዳድሩት? አገሪቱ እንደገና ከዜሮ ልትጀምር ማለት እኮ ነው፡፡ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የዓለም አገራት በቴክኖሎጂ ዕድገት በሚወዳደሩበት ጊዜ እኛ ደግሞ ጭራሽ የነበሩትን ማውደማችን እንዴት መሳለቂያ አያደርገንም ታዲያ? ሕዝብ የሚጠቅመውንና የሚጎዳውን ለይቶ ማወቅ አለበት እንጂ በማንም ግፊት የሚነዳ ከሆነ የራሱን ንብረት ራሱ እያወደመ፣ የራሱን ወገን ራሱ እያጠፋ ነው ማለት ነው፡፡
ከምንም በላይ ደግሞ የነገ የአገር ተረካቢ ናቸው የሚባሉትን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ልምድ እያበላሸን ነው፡፡ አንድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ አገሩን ማወቅ የሚጀምረው ከዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ አንድ የ12ኛ ክፍል ፈተና የወሰደ ተማሪ በጣም የሚያጓጓው ነገር ቢኖር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ገብቶ ‹‹ትንሿ ኢትዮጵያ›› የምትባለዋን ማየት ነው፡፡ ከእሱ በፊት የነበሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሚነግሩት ሁሉ ይቀናል፡፡ ምክንያቱም የሚነግሩት ከፍተኛ ፍቅርና መነፋፈቅ እንዳለ ነው፡፡ አሁን ግን ዘረኝነትን በሚነዙ ሰዎች ይህ እየተሸረሸረ ነው፡፡ ይህ ለምን ይሆናል? የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ማለት ብዙ ነገር የሚያውቅ ነው፡፡ እንዴት በማንም አሉቧልታ ከወንድሙ ጋር ድንጋይ ይወራወራል?
ለመሆኑ ግን መንግስትስ ወጣቶች አገራቸውን እንዲያውቁ የሚያስችል ምን ሥራ ሰርቷል? ወጣቶችን በጋራ ጉዳይ ላይ የሚያወያዩ መድረኮች ነበሩ ወይ? በሥርዓተ ትምህርት ላይም ይሁን በመልካም አስተዳደር ላይ ከወጣቶች ጋር በቅርበት ተሰርቷል? የሚሉት ጥያቄዎች መንግስት ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ ናቸው፡፡ በተለይም በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ በጥሩ ስነ ምግባር የታነፀ ወጣት እንዲፈጠር የሚያስችል ሥራ መሰራት አለበት፡፡ በተለያዩ ሱሶች የተጠመደ ተማሪ ማፍራት የለብንም፡፡ መጠጥ ቤቶችና የጫት መቃሚያ ቤቶች ከዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ምን ያህል የራቁ ናቸው? ለአገሪቱ ሰላምና ብልጽግና መሥራት የሁላችንም ኃላፊነት ነው፡፡ ከአመራሮቹ መታደስ ጋር ህዝብም መታደስ አለበት፡፡ በተለይም ሕዝቡ በውጭ ባሉት አካላት መነዳት የለበትም፡፡ እኛ ከታደስን እነርሱንም ልክ ማስገባት እንችላለን፡፡ ስለዚህም መታደሱ የሁላችንም መሆን አለበት፡፡

ዋለልኝ አየለ 

Published in አጀንዳ
Wednesday, 10 January 2018 16:29

ክፋት ጎረቤት እስከ ማጣት

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጀመር ግብፅ ክፉኛ ራሷን ታመመች፡፡ ለዓመታት ስታዝበትና ስትፈነጭበት የነበረው አባይ በኢትዮጵያ ለልማት ይውላል ብላ አስባ አታውቅምና ህመሙ በረታባት፡፡ ግንባታውን ለማስቆም ያልፈነቀለችው ድንጋይ፤ ያልሄደችበት መንገድ የለም፡፡
አሁን በእስር ላይ የሚገኙት መሃመድ ሙርሲ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማስተባበር የኃይል እርምጃም እንደሚወስዱ ዛቱ፡፡ የኢትዮጵያን ልማትና ዕድገት የማይሹ ኃይሎችን ያለምንም ምርጫና ቅድመ ሁኔታ እንደሚረዱም አስታወቁ፡፡ይህ ሃሳብ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስትም በተለያየ መንገድ እያራመደ መሆኑ ለማንም ግልፅ ነው።ምንም እንኳን የማይሳካ ቢሆንም።
በቅርቡ ደግሞ ጠንካራ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሌለውን የኤርትራ መንግስት ጋር ትብብር በመፍጠር እስከ 30 ሺህ የሚደርሰውን ጦሯን በኤርትራ ለማስፈር ማቀዷን አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ይገኛሉ። የኤርትራ መንግስትም ሃሳቡን ‹‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ›› ብሎ ያለማመንታት መቀበሉ ተዘግቧል፡፡
ይህ እርምጃ ታዲያ ግብፅ ወደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ለምታደርገው የማደናቀፍ ጉዞ መልካም አጋጣሚ ሊፈጥርላት ስለሚችል በኢትዮጵያ በኩል ተገቢው ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ በርካቶች ያሳስባሉ፡፡ ለኢትዮጵያ ውድቀት የሚተጉ አካላትን በማሰልጠንና በመደገፍ የተጠመደው የኤርትራ መንግስት የአገሪቱን ልማት ለማደናቀፍ የምትጥር አገርን ጦር መቀበሉ ብዙም ባይደንቅም ጉዳዩን በትኩረት መከታተል እንደሚሻ ማሳያ ነው፡፡ ይህ ሂደት መንግስትና ህዝብ በአንክሮ ሊከታተሉት ይገባል።
የሻዕቢያ መንግስት የጥፋት ተግባርና ባህርይው ከጎረቤቶቹ ጋር እያፋታው ብቻውን እያስቀረው ነው፡፡ ሰሞኑን ሱዳን ከኤርትራ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር ለመዝጋት መወሰኗ የዚሁ ማረጋገጫ ነው፡፡ ሱዳን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችና የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በከሰላና ኮርዶፋን ግዛቶች ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጇን ተከትሎ ነው ድንበሩን የዘጋችው፡፡ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያው የሚገባው በዚሁ ድንበር በኩል በመሆኑ ሱዳን ድንበሩን ለመዝጋት ተገዳለች፡፡ የህገ ወጥ ድርጊቱ ዋና ተዋናይ የሻዕቢያ መንግስት መሆኑም ፀሃይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ ስለሆነም ከፍለ አህጉሩን በማወክ ላይ የሚገኘው ስርዓት አደብ ሊገዛ ይገባዋል። ጎረቤቶቿን እየነከሰችና እያስነከሰች የዘለቀችው ኤርትራ ሁሉም ‹‹ዓይንሽን ለአፈር እያሏት›› ነው፡፡ ሁሉም ‹‹ክፉ ጎረቤት ምን ሊበጀን›› እያሏት መራቅን መርጠዋል፡፡ የሱዳን እርምጃ ከዚህ ውጭ ሌላ ምንም ሊባል አይችልም፡፡ ክፉ ጎረቤትን ማንም አይወደውም፣አይቀርበውም፡፡
ለቀጣናው ሠላም ማጣት ተግታ የምትሰራው ኤርትራ ሶማሊያን እያተራመሰ የሚገኘውን አልሻባብን ትደግፋለች በሚል የመንግስታቱ ድርጅት በተደጋጋሚ ማዕቀብ ጥሎባታል፤ ማዕቀቡንም አራዝሟል፡፡ ኤርትራ ግን ድርጊቷን በማመን ከሠላሙ መንገድ ይልቅ የክፋቱን ጎዳና መርጣለች፡፡
ባለፈው ዓመት ህዳር ወር እንኳ 113 ታጣቂዎች ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ሰርጎ ለመግባት ሞክረው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል፡፡ ሻዕቢያና ደጋፊዎቹ የኢትዮጵያን ሰላምና ልማት ለማደናቀፍ ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም፡፡
የጥፋት ኃይሎች መናኸሪያና መሸሸጊያ በመሆንም የጎረቤቶቿን ሠላም ለማናጋት ሌት ተቀን ብትተጋም አልተሳካላትም፡፡ ኢትዮጵያ ለሠላም ድርድር ፅኑ ፍላጎት እንዳላት በተደጋጋሚ ብትገልፅም ለሠላም ድፍን የሆነው የኢሳያስ መንግስት ጆሮ አልሰጣትም፡፡
ይልቁንም ጠላቶቿንና ብሔራዊ ጥቅሟን ለማሳጣት የሚተጉ እንደነ ግብፅ ያሉ አገራትና አካላትን በጉያው መሸሸግን መርጧል፡፡ ኢትዮጵያን ለማጥቃት ለሚፈልጉ ሁሉ በሬ ክፍት ነው ብሏል፡፡ ይህ እኩይ ድርጊቱ ጎረቤት አልባ ከማድረግ ውጭ አንዳችም የሚጠቅመው ነገር እንደሌለ ግልፅ ነው፡፡ በክፋት ተሞልቶ፤ ለክፋት ተልዕኮዎች የሚተጋው ሻዕቢያ ከጎረቤቶቹ ተጣልቶ ብቻውን እስከ መቼ ድረስ ሊጓዝ ይችል ይሆን?

Published in ርዕሰ አንቀፅ

ከኢንዱስትሪዎች የሚለቀቁ በካይ ጋዞች ለአየር ንብረት ለውጥ ትልቁን ድርሻ ያበረክታሉ፤

አዲስ አበባ፤- የአየር ንብረት ለውጥ ድርድርና በድርድር የሚገኘውን ውጤት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ማሰልጠኛ ማዕከል በኢትዮጵያ ሊከፈት መሆኑን የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የአየር ንብረት ለውጥ ትግበራ ማስተባበሪያ ጀኔራል ዳይሬክተር አቶ ደባሶ ባይለየኝ፤ በኢትዮጵያ ሀላፊነት የሚከፈተው ማዕከል በዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተደራዳሪዎች የድርድር አቅማቸውንና ክህሎታቸውን ለማሳደግ እና በድርድር የሚገኘውን ውጤት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አቅምን ለመገንባት የሚረዳ መሆኑን ለአዲስ ዘመን ተናግረዋል።
በዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ አገራት የድርድር አቅማቸውን ማሳደግ ካልቻሉ የአባል አገራትን ጥቅም ቀርቶ የብሔራዊ ጥቅማቸውን ፍላጎት ማሳካት አይችሉም ይላሉ። የአገራቸውንና የፎረም አባላቱን ጥቅም ለማስከበር፤ በአገራቱ ተደራዳሪዎች ያለውን የተለያየ አቅም ማዕከሉ ተቀራራቢ የሆነ እውቀትና ክህሎት እንዲገነቡ እንደሚረዳቸው አቶ ደባሱ ተናግረዋል፡፡ ይህም በድርድሩ አገራዊና ቡድናዊ ጥቅምን በማስተሳሰር በድርድር መድረኮች ወጤታማ ስራ ለማከናወን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡
በድርድር ውጤት ማግኘት ብቻ ሳይሆን ከስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮችን ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ እውቅትና ክህሎት እንደሚጠይቅ ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ ማዕከሉ ከድርድር የሚገኙ ውጤቶችን መነሻ አድርጎ ለመተግበር ዝግጁ የሚያደርጉ ስልጠናዎችን ለመስጠት በሚያስችል መልኩ ተቋቁሟል ብለዋል።
ማዕከሉን የማቋቋም ሀላፊነቱን የወሰደው ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው የተለያዩ መዋቅሮችን የመዘርጋትና ስርዓተ ትምህርት እንዲዘጋጅ ማድረጉንም ነው የጠቆሙት፡፡ የማሰልጠኛ ማዕከሉ በከፍተኛ እና በዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ አገራት ሚኒስትሮች በተገኙበት በአዲስ አዲስ በይፋ ተቋቁሞ እውቅናም ሰጥተውታል።
ማዕከሉ በቀጣይ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስር ሆኖ ራሱን የቻለ ዓለም አቀፍ ተቋም እንዲሆን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ጋር በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው ለትግበራ የሚሆኑ አስፈላጊ ሰነዶች ተዘጋጅተዋል ብለዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ እራሱን የቻለ ተቋም ሆኖ ከጸደቀ በኋላም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማስተዋወቅ ሥራ ይሰራል ተብሏል፡፡
በማዕከሉ አስተባባሪነት በዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ 51 ወጣት ተደራዳሪዎች ከአሜሪካ ፊሌቸር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር አጭር ስልጠና ተሰጥቷል። በአሁን ወቅትም ከጣሊያን መንግስት ጋር በመተባበር 100 ለሚሆኑ ሰልጣኞች ተመሳሳይ ስልጠና ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነው። የፈረንሳይ መንግስትና ሌሎች አገራት ለማዕከሉ እውቅና በመስጠት ለመደገፍ ቃል ገብተዋል።
ኢትዮጵያ በዝቅተኛ እና በከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ፎረሞች ሊቀመንበር ነች፡፡

አጎናፍር ገዛኸኝ 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 3

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።