Items filtered by date: Thursday, 11 January 2018

 ኢትዮጵያዊው አትሌት አበረታች መድሃኒት ተጠቅሞ በመገኘቱ ቅጣት እንደተላለፈበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት አስታወቀ። አትሌቱ ከማንኛውም ስፖርታዊ ውድድሮች  ለአራት ዓመታት እንዳይሳተፍ የሚያደርግ እገዳም ነው የተላለፈበት።

በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬ ሽኖች ማህበር እገዳው የተላለፈበት አትሌት ሐይሌ ቶሎሳ የሚባል ሲሆን፤ እአአ ግንቦት 15 ቀን 2016 ፔሩ ላይ በተካሄደው የሞቪስታር ሊማ የማራቶን ውድድር ላይ ተሳትፏል። በወቅቱ በዓለም አቀፉ የፀረ አበረታች መድሃኒቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ በተካሄደው የላብራቶሪ ምርመራም አትሌቱ Benzoyl ecgonine and Methylecgonine (Cocain Metabolites) የተባለውንና በዓለም አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች የተከለከሉ መድኃኒቶች ዝርዝር ውስጥ የተካተተውን ቅመም መጠቀሙ ተረጋ ግጧል። ኤጀንሲው የስፖርት የፀረ-አበረታች ቅመሞች ህግ ጥሰት መፈፀሙን በመግለጽም ማህበሩ በአትሌቱ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ አሳውቋል።

 የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች  ጽሕፈት ቤትም የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ማህበራት ፌዴሬሽን (IAAF) የላከውን መረጃና የውሳኔ ሃሳብ መነሻ በማድረግ አትሌቱ የህግ ጥሰቱን የማጣራት ሂደቱ ከተጀመረበት እአአ ከግንቦት 15 ቀን 2016 ጀምሮ እስከ ግንቦት 15 ቀን 2020 ለአራት ዓመታት በማንኛውም ሃገር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮች እንዳይሳተፍ ቅጣት አስተላልፏል።

የስፖርት አበረታች ቅመሞችን ወይም ዶፒንግን በመጠቀም ያልተገባ ውጤት የማስመዝገብ ችግር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሃገራችን ስፖርት በተለይም የአትሌቲክሱ ስጋት እየሆነ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅሕፈት ቤት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 400/2009 ራሱን ችሎ የተቋቋመ ሲሆን፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ቀደም ሲል ጀምሮ የፅሕፈት ቤቱን አደረጃጀት በሰው ኃይል ማጠናከርን ጨምሮ የተለያዩ የአሠራር ስርዓቶችን የመዘርጋት፣ የትምህርትና ስልጠና፣ የምርመራና ቁጥጥር እንዲሁም በየደረጃው ዓለም አቀፍ ግንኙነቱን የማጠናከር ተግባራት ትኩረት ተሰጥቷ ቸው በመከናወን ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ፅሕፈት ቤቱ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የስፖርት የፀረ-አበረታች ቅመሞች ወይም የዶፒግ የህግ ጥሰት በሚፈፅሙ አካላት ላይ አስፈላጊው የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በቀጣይም አገር አቀፍ የስፖርት ማህበራትንና ሌሎችንም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው የፀረ-ዶፒንግ እንቅ ስቃሴ በተለይም የህግ ጥሰት በሚፈፅሙ አካላት ላይ የሚወሰደው የእርምት እርምጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ጽህፈት ቤቱ አሳውቋል፡፡

   ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትም ከዶፒንግ ነፃ የሆነ ስፖርት በማስፋፋት በትክክለኛው መንገድ ተወዳድረው የሚያሸንፉ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩላቸውን ገንቢ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ብርሃን ፈይሳ

 

Published in ስፖርት

ከወጣት አሰልጣኞች ተርታ ይሰለፋል፡፡ እንደ ብዙሐኑ የስፖርት ሰዎች ወደ እግር ኳሱ የገባው በልጅነቱ ከአብሮ አደጎቹ ጋር የጨርቅ ኳስ በመግፋት ነው፡፡ ካደገበት ቢሾፍቱ ከተማ እስከ ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊነት የደረሱ እግር ኳስ ተጫዋቾች ወጥተዋል፡፡ እርሱ ግን ጉዳት በተጫዋችነት ብዙ እንዳይገፋ አድርጎታል፡፡ ጉዳቱን ተከትሎ ጫማውን የሰቀለው ፍሬው በተቃራኒው ብዕሩን በማንሳት የስፖርት ሳይንስ ትምህርት በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ መማር ጀመረ፡፡ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ አካባቢው ላይ ወጣቶችን ሰብስቦ ሲያሰለጥን በመቆየት፤ ለብሔራዊ ቡድን ተመራጭ እስከመሆን የደረሱ እንደ አቤል ማሞ እና ሌሎች ተጫዋቾችን ለማሰልጠን ችሏል፡፡
የተለያዩ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ቢሾፍቱ ከተማን ለክረምት ወራት ቅድመ የውድድር ዝግጅት የሚመርጧት በመሆኑ የሚያ ሰለጥናቸውን ልጆች ከፕሪምየር ሊግ ክለቦች ጋር የወዳጅነት ጨዋታ እንዲያደርጉ ዕድል አመቻችቶላቸዋል፡፡ ክለቦቹም የተሻለ ተስፋ ያላቸውን ወጣቶች እየወሰዱ ዕድል ይሰጧቸው ነበር፡፡ ይሄን የተመለከቱ የስፖርት ሰዎችም ፍሬውን ወደተሻለ ደረጃ ሊያሸጋግር የሚችል የአሰልጣኝነት ዕድል ፈጠሩለት፡፡
በ2008 ዓ.ም ደደቢትን በአሰልጣኝነት በመቀላቀል የሴት እግር ኳስ ክለብ ማሰልጠን ጀምሯል፡፡ በክለቡ ብዙም ሳይቆይ የሁለት ዋንጫዎች ባለቤት ማድረግ በመቻሉ የዓመቱ ኮከብ አሰልጣኝ ለመባል በቅቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የሲዳማ ቡና ሴት እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ በመሆን እየሠራ ይገኛል፡፡ በአሰልጣኝነት ጉዞ እና በአገሪቱ የሴቶች እግር ኳስ ደረጃ ዙሪያ ከአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል አጭር ቆይታ አድርገናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወደ አሰልጣኝነት የገባኸው የስፖርት ሳይንስን በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ተምረህ ነው፤ ሳይንሱን መማርህ አሁን ለምትገኝበት አሰልጣኝነት ሕይወት ጠቅሞሃል?
አሰልጣኝ ፍሬው፡- ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ መማር ሰውን ይለውጣል፡፡ የድሮ እናቶች የሚወልዱት በቤት ነበር፤ አሁን ተቀይሯል፡፡ አሁን ምጧ የደረሰ እናት ወደ ሆስፒታል ነው የምትወሰደው፡፡ ምክንያቱም የሚመጣው አይታወቅምና በዘመናዊ ነገር ታምናለህ፡፡ በእርግጥ ድሮ ጥራት ያላቸው ብዙ ተጫዋቾች ነበሩ፡፡ ነገር ግን የእግር ኳስ ሳይንሱ ድሮ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ሳይንሱ ብቃት ያላቸውን ተጫዋቾች ይበልጥ ለማውጣት ያግዛል፡፡ ሳይንሱ በአብዛኛው ተጫዋቾች ከልጅነታቸው ጀምሮ ብቃታቸውን አውጥተው እንዲያድጉ ያደርጋቸዋል፡፡ አሁንም ቢሆን እኔ ወደ ሲዳማ ቡና የገባሁት በወጣቶች ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ ከክለቡ ሃላፊዎች ጋር ተግባብቼ ነው፡፡
በእርግጥ በደደቢት ክለብ ሻምፒዮን ሆኜ ወደ ሲዳማ ቡና ስገባ በወጣቶች ላይ መስራቱ የሚፈጥረው ስጋት አለ፤ ምክንያቱም ሻምፖዮን ሆነህ ስትሄድ ሁሉም ስሙን መጠበቅ ይፈልጋል፡፡ እግር ኳስ ውለታ አያውቅም፡፡ ነገር ግን የክለቡ ፕሬዚዳንት ጋር ባደረግነው በቂ ውይይት ለማሰልጠን ተረክቤያለሁ፡፡ ሳይንሱን ለመማር የወሰንኩትም የኢትዮጵያ የሴቶችንም ሆነ የወንዶች ሊግ በቅርበት እከታተል ስለነበረ ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በየትኛውም ደረጃ በተማሩ ሰዎች መመራት እንዳለበት አምናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሴቶች እግር ኳስ ላይ መስራት ለምን ምርጫህ አደረግክ?
አሰልጣኝ ፍሬው፡- በወንዶችም በሴቶችም እግር ኳስ ላይ ብትሰራ አሰልጣኝነት ሁሌም ያው ነው፡፡ ለውጥ የለውም፡፡ ሴቶች እግር ኳስ ላይ የሚገባውን ያህል አልተሰራም እንጂ ቢሰራ ኖሮ ከወንዶች ያልተናነሰ አቅም አላቸው፡፡ ሴቶች ታክቲካል የሆኑ ስልጠናዎችን የመረዳት አቅማቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ስልጠናን የመረዳት አቅማቸውና ስነምግባራቸውም በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በደደቢት በነበረኝ ቆይታም እነ ወይንሸት፣ ብርቱካን፣ ሎዛ፣ ውባለም እንዲሁም ኤደን የነበራቸው የታክቲክ አረዳድ ከፍተኛ እንደነበር አስተውዬአለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሴቶች ከወንዶች የተሻለ የታክቲክ አረዳድ ካላቸው የሴቶች እግር ኳስ ለምን በዚያው መጠን መሻሻል አላሳየም?
አሰልጣኝ ፍሬው፡- አንድ ወላጅ ቤተሰቡን በአግባቡ መምራት ካልቻለ ችግሩ የልጆቹ ሳይሆን የወላጅ ነው፡፡ ምንም ያህል እውቀቱ ቢኖርም እግር ኳስ ላይ ከታች ጀምሮ ካልተሰራ በስተቀር ስፖርቱን ማሳደግ አይቻልም፡፡ ተጫዋቾቻችን ሁሉም ነገር እያላቸው እግር ኳሱ ላይ ባሉ የመሪዎች ችግር ምክንያት አላደገም፡፡ ይህም የሴቶቹ ጥረት ፍሬ እንዳያፈራ ያደርገዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንዳጠቃ ላይ የሴቶች እግር ኳስ በተለይም ከብሔራዊ ቡድን ውጤት አንፃር አሁን በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አሰልጣኝ ፍሬው፡- የሴቶች እግር ኳስ በተመለከተ በብሔራዊ ቡድንም ይሁን በክለብ ደረጃ የሚሰጠው ትኩረት እጅግ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ የወንዶች ክለብ ከሌለ የሴቶች ክለብ የማይኖርበት ሁኔታ ይበዛል፡፡ በእርግጥ አሁን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወንዶቹን ቡድን ሲበትን የሴቶችን ቡድን ማቆየቱ እንደ መልካም ተሞክሮ ሊወሰድ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሴቶች ቡድን የሚሰጠውን አይነት ትኩረት ሌሎች ክለቦችም መስጠት አለባቸው፡፡ በክለብ ደረጃ የሴቶች እግር ኳስ በራሱ መቆም አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሴቶች እግር ኳስ የክለቦች ውድድር በየጊዜው የሚኖረው መሻሻል አጠያያቂ ቢሆንም በውድድር ደረጃ ሳይቋረጥ ዘልቋል፤ ይሄ ምን ያህል እግር ኳሱን ጠቅሞታል?
አሰልጣኝ ፍሬው፡- ውድድሩ መኖሩ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ይበልጥ ትኩረት ይፈልጋል፡፡ በፉክክሩ ላይ የተመጣጠነ ትኩረት የለም፡፡ አንዳንዶቹ ክለቦች ከትጥቅ ጀምሮ የሚያስፈልጓቸው ግብዓቶች ተሟልቶላቸው የሚወዳደሩ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ ግን ተመጣጣኝ ያልሆነ አነስተኛ ትኩረት ያገኛሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ዞሮ ዞሮ ብሔራዊ ቡድኑ ላይ የሚፈጥረው ጫና ቀላል አይደለም፡፡ በብሔራዊ ቡድን የሚመጣው ውጤት የክለቦች ነፀብራቅ ነው፡፡ ክለብ ላይ ጥሩ ውድድር ሳታደርግ የምትመጣ ተጫዋች ብሔራዊ ቡድን ላይ የሚፈለግባትን አስተዋፅኦ ልታበረክት አትችልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሰልጣኝነት ቆይታህ ክልሎች ብቁ ተጫዋቾችን ከማፍራት አንጻር የሚያደርጉትን ጥረት እንዴት ትመዝነዋ ለህ?
አሰልጣኝ ፍሬው፡- ሁሉም ክልሎች የበኩላቸውን ጥረት ያደርጋሉ፡፡የሴቶችን ፕሪምየር ሊግ ከተመለ ከትከው ግን አብዛኞቹ ተጫዋቾች ከደቡብ ብሄርና ብሄረሰቦች ክልል የመጡ ናቸው፡፡ በደደቢት እና ንግድ ባንክ ክለቦች ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተጫዋቾች ከዚህ ክልል ወጥተዋል፡፡ ክልሉ ውስጥ እግር ኳስ ባህል ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም ዘላቂነት ላይ ብዙ መስራት ይጠይቃል፡፡ አምና ከክልሉ ወረዳ የተወጣጡ 17 ልጆችን ይዤ ነው ስሳተፍ የነበረው፡፡ በዚህ ዓመት ደግሞ ስድስት ልጆች ጨምሬ በአጠቃላይ ከ28 ተጫዋች 23 ልጆች ከወረዳ ነው ያሳደኩት፡፡ ከነዚህም ውስጥ ደግሞ የተሻለ ብቃት ያላቸው ልጆች የተሻለ ክፍያ ወዳላቸው ክለቦች ተዘዋውረዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ጊዜ በጣም አመሰግናለሁ !
አሰልጣኝ ፍሬው፡- እኔም አመሰግናለሁ !

Published in ስፖርት
Thursday, 11 January 2018 20:08

ከመቃሚያ ወደ መቋሚያ

‹‹መቋሚያ›› የድርጅቱ ስም ነው፡፡ የዚህ ድርጅት መስራች ለ13 ዓመታት ያህል በሱስ ውስጥ መቆየቱን ይናገራል፡፡ አሁን ግን ይሄ ወጣት ከሱስ ተላቆ ውሎውን ከመቃሚያ ቤት ወደ ‹‹መቋሚያ›› ቤት አሸጋግሯል፡፡ ‹‹መቋሚያ›› ማለት ምርኩዝ ማለት ነው፤ ድጋፍ የሚያስ ፈልጋቸው ሰዎች የሚደገፉት፡፡ መቋሚያ ድርጅትም እንዲሁ ሱስ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ከሱስ እንዲወጡ የሚሠራና ድጋፍ የሚያደርግ ነው፡፡ ድርጅቱ እንዴትና መቼ ተመሰረተ? ምንስ እየሠራ ነው? በሚለው ዙሪያ ከድርጅቱ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ወጣት ኤልያስ ካልአዩ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡
ለ13 ዓመታት ያህል በሱስ ውስጥ የቆየው ወጣት ኤልያስ በ2000 ዓ.ም ያለበትን ሱስ እርግፍ አድርጎ መተው ፈለገ፡፡ ነገር ግን ዝም ብሎ መተውን ብቻ አልመረጠም፡፡ ይልቁኑም ሱስ በሰው ልጆች ላይ የሚያስከትለውን ከፍተኛ ችግር በመገንዘብ በሌሎች ወጣቶች ላይም ‹‹ይብቃ›› የሚለውን መልእክት ማስተላለፍ ጠቃሚ መሆኑን አመነ፡፡ ለዚህም መጀመሪያ በክበባት ላይ እየተሳተፈ ማስተማር ጀመረ፡፡ በኋላም በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ‹‹መቋሚያ›› የተባለ ድርጅት መሰረተ፡፡ ይህን ድርጅት ሲመሰርት የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍ አደረገለት፡፡ እስካሁንም ድጋፉ አልተቋረጠም፡፡
ድርጅቱ ውጤታማ እየሆነ በመሄዱ በፌዴራል ደረጃ ህጋዊ ሰውነት አግኝቶ ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ጋር መሥራት ጀመረ፡፡ እንደ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የመሳሰሉት ተቋማት አብረውት ይሰራሉ፡፡ መጀመሪያ አካባቢ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲና በመቀሌ ከተማ አካባቢ በተለያየ መንገድ ሲያስተምር ቆይቷል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና በጎዳናም ላይ አውደ ርዕይ እያዘጋጁ ከወጣቶች ጋር በጋራ ትምህርት ይሰጣሉ፡፡
በመቋሚያ ድርጅት ውስጥ ያሉ ወጣቶች ሱስ ውስጥ የነበሩና ከሱስ መላቀቅ የቻሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ወጣቶች ስለ ሱስ አስከፊነት ሲናገሩ ተሰሚነት ይኖራቸዋል፡፡ መውጣት እንደሚቻልም ማረጋገጫ ይሆናሉ፡፡ ድርጅቱ የህክምናና የምክር አገልግሎት ይሰጣቸዋል፡፡ በተለይም የምክር አገልግሎቱ ሱስ ውስጥ ቆይተው መተው የቻሉ ወጣቶች ሱስ ውስጥ ላሉት የሚሰጡት ነው፡፡
የትግራይ ክልል በሱስ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መሥራቱ ደግሞ ድርጅቱ ስኬታማ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ እነ ወጣት ኤልያስ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እያሉ ይህን ሥራ ሲሰሩ የመቀሌ ከተማ አስተዳደር ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመሆን ድጋፍ ያደርግላቸዋል፡፡ በከተማዋ ውስጥ ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ዩኒቨርሲቲውም ሆነ የከተማ አስተዳደሩ በጋራ በመስራታቸው በከተማዋ ውስጥ ለውስጥ ማምጣት ተችሏል፡፡ በዚህ ሥራም የመቀሌ ከተማም ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል፡፡
በመቋሚያ ድርጅት ውስጥ ትልቁን ሚና የሚጫወቱት ቀድሞ ሱሰኛ የነበሩና አሁን ከሱስ የወጡ ወጣቶች ናቸው፡፡ እነዚህን ወጣቶች እንዴት ማሳመን እንዳለባቸው ያውቃሉ፡፡ በሱስ ውስጥ ያሉ ወጣቶችን ስነ ልቦና በሚገባ ያውቁታል፡፡ ከምንም በፊት መጀመሪያ የሚያደርጉት የማሳመን ሥራ ነው፡፡ አንድ ሰው ዝም ብሎ ተነስቶ ‹‹ጫትና ሲጋራ ጎጂ ነው›› ከሚላቸው ይልቅ ውስጡ የነበረ ሰው ምን ይደርስበት እንደነበር ሲነግራቸው ተጸጽተው ይመለሳሉ፡፡ እንዲህ ሲሆን አንዱ ለአንዱ መቋሚያ ወይም ምርኩዝ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ወጣት ኤልያስ መቋሚያ ድርጅትን ሲያቋቁም ‹‹አገር ማለት ሰው ነው›› የሚል ፍልስፍና መርሁ በማድረግ ነው፡፡ ሰው ማለት ደግሞ የከበረ አዕምሮ ባለቤት ነው፡፡ የዚህ ፍልስፍና ታሳቢነት አገር ማለት ጤናማ የሆነ ትውልድ ሲኖራት መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ በተለይም አምራች የሆነው ወጣቱ ክፍል ጤናማ መሆን አለበት፡፡ በሱስ ውስጥ ያለ ወጣት ግን በብዙ ችግሮች የተተበተበ ነው፡፡ ለ13 ዓመታት ያህል በቆየበት ሱስ ውስጥም ይህን በሚገባ አይቷል፡፡ የሱስ አደገኛነት አካላዊ ጤንነትና ኢኮኖሚ ብቻ አይደለም፡፡ በሱስ ውስጥ ያለ ወጣት ነጻ ሆኖ ማሰብ አይችልም፡፡ አካባቢና አገሩን በአግባቡ መመልከት አይችልም፡፡
የሰው ልጅ የማሰቢያ የአካል ክፍሉ አንጎል ነው፡፡ ሁሉም የሰውነት ክፍል የሚታዘዘው በአንጎል ነው፡፡ እያንዳንዱ አደንዛዥ ዕፅ ደግሞ ጉዳት የሚያደርሰው እዚህ የሰው ልጅ መሰረታዊ የአካል ክፍል ላይ ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው የአዕምሮ ጤና ማለት አንድ ሰው ያለውን ብቃት ተጠቅሞ በአካባቢው ካሉ ሰዎች ጋር መልካም የሆነ ግንኙነት መፍጠር ሲችል ነው፡፡
የድርጅቱ መርህ ለአገር ግንባታም ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለው ነው የሚያምኑት፡፡ አንድ ወጣት በተሰማራበት ዘርፍ ውጤታማ የሚሆነው ነጻ የሆነ አዕምሮ ሲኖረው ነው፡፡ የትኛውም ሥራ አይነት የሚሰራው በአዕምሮ ነው፡፡ የጉልበት ሥራም ቢሆን ሰውነት የሚታዘዘው በአዕምሮ ነው፡፡ ሱስ ውስጥ ያለ ሰው አካላዊ ሰውነቱ ብቻ ሳይሆን ውስጣዊ አስተሳሰቡንም ይጎዳዋል፡፡ ጭንቀት፣ መረበሽ፣ መነጫነጭ፣ ራስን መጥላትና መሰላቸት የሱስ ባህሪዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች ባሉበት ሱሰኛ ሰው በሥራ ላይ ውጤታማ አይሆንም፡፡ በሥራ ላይ ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ ግንኙነት ውስጥም አሉታዊ ጫና ይኖረዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት እ.አ..አ 2013 ባወጣው መረጃ መሰረት በዓለም ላይ በሱስ ምክንያት በየደቂቃው ሦስት ሰዎች ሲሞቱ አሥር ሰዎች ለአካላዊ ጉዳት ይጋለጣሉ፡፡ ይህ ችግር ከተጋረጠባቸው አህጉራት ደግሞ አንደኛዋ አፍሪካ ነች፡፡ አብዛኞቹ ደግሞ ወጣቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ወጣቶች ነገ አገር የሚረከቡ ናቸው፡፡ ያለ ጤና ሰው ሊሰራ አይችልም፤ ያለ ሥራ አገር ልታድግ አትችልም፡፡ የአገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥራ ሊሰራ አይችልም፡፡
በሱስ ምክንያት ብዙ ወጣት የጀመረውን ሥራ ከዳር ሳያደርስ አቋርጧል፤ ትምህርት ጥሎ ወጥቷል፡፡ ጤናቸውን አጥተው ለወላጆቻቸው ሥጋት ሆነዋል፡፡ እየባከነ ያለው የሰው ልጅ አዕምሮ ነው፡፡ ለዚህም መቋሚያ በዋናነት መሰረት አድርጎ እየሠራ ያለው ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ነው፡፡ መቀሌ ላይ የተጀመረው ይህ የመቋሚያ እንቅስቃሴ አሁን ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም እየሄደ ነው፡፡ በሀረማያ ዩኒቨርሲቲም በተመሳሳይ መቋሚያ ተጀምሯል፡፡ በድሬዳዋ፣ አዳማና ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዎችም ተጀምሯል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ድርጅቱ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ እያስተማረ ይገኛል፡፡ ከዚህ በፊትም በባህርዳር፣ ጎንደርና ወልዲያ ዩኒቨርሲቲዎች በመሄድ ከተማሪዎች ጋር በመገናኘት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ አከናውኗል፡፡
ድርጅቱ 450 ያህል ወጣቶችን ከሱስ አውጥቶ ነጻ ማድረግ ችሏል፡፡ እነዚህ 450 ወጣቶች አሁን ሌሎች ወጣቶችን እያስተማሩ ነው፡፡ ሁሉም በሱስ ውስጥ የነበሩ ናቸው፡፡ የእነዚህ ወጣቶች ወላጆች በድርጅቱ ተደንቀዋል፡፡ ለልጆቻቸው ተስፋ የቆረጡ ነበሩ፡፡ አሁን ግን እናትና አባት ከልጆቻቸው ጋር ቁጭ ብለው መጫወት ጀምረዋል፡፡ በሱስ ምክንያት ወደ ጎዳና ሕይወት ወጥተው የነበሩ ልጆች ተመልሰዋል፡፡ በዚህም እነ ኤሊያስ ከፍተኛ ደስታ ይሰማቸዋል፡፡ እንኳን 450 አንድ ሰው እንኳን ወደ ሕይወት መመለስ ትልቅ የህሊና እርካታ ይሰጣል፡፡
ይህን የፀረ ሱስ ዘመቻ ለማጠናከር የግንዛቤ ለውጥ ዋናው ጉዳይ ቢሆንም፤ ከልካይ ህጎችም መኖር እንዳለባቸው የድርጅቱ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ወጣት ኤልያስ ይናገራል፡፡ በተለይም በትምህርት ተቋማት አካባቢ መጠጥ ቤቶችና ጫት ቤቶች ሊከለከሉ ይገባል፡፡ የወጡ ህጎችም ተግባራዊ መሆን አለባቸው፡፡ ይህም ውጤታማ እንደሚያደርግ መቀሌ አካባቢ የተደረገው ነገር ምስክር ይሆናል፡፡
የመቋሚያ ድርጅት አባቶች የውጭ ወራሪን ተከላክለው ነጻ እንደወጡ ሁሉ የአሁን ወጣቶች ደግሞ ሱስን ተከላክለው ነጻ ከወጡ የበለጸገች አገር ይፈጥራሉ የሚል አላማ የሰነቀ ነው፡፡ የዓድዋ ጀግኖች ታሪክ እንደሰሩት ሁሉ ሱሰኝነትን በማጥፋትም ትልቅ ታሪክ መደገም ይቻላል የሚል አቋምም አላቸው፡፡

ዋለልኝ አየለ

Published in ማህበራዊ
Thursday, 11 January 2018 20:06

ሁሉም ያሸነፈበት መድረክ

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለ17 ቀናት ያካሄደው ስብሰባ ማጠቃለያ ላይ በአወጣው መግለጫ የአራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች አመራሮች የሰጡትን ማብራሪያ በተከታታይ ስናቀርብ ቆይተናል። በዛሬው ዕለት የድርጅቶች አመራሮች ለተፈጠሩ ችግሮች የሚወሰደውን ሃላፊነት፣ በመድረኩ ማን አሸነፈ ? ኢህአዴግ ከችግሩ ይወጣል? በሚሉ ጥያቄዎች ዙሪያ የሰጡትን ማብራሪያዎች ይዘን ቀርበናል።
ለተፈጠሩ ችግሮች የሚወሰደውን ሃላፊነት በተመለከተ የደኢህዴንና ኢህአዴግ ሊቀመንበር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዳብራሩት በእርግጥም በእኛ የሥራ አስፈጻሚ ግምገማ ወቅት ከልብም የተመለከትነው ነገር ቢኖር እነዚህ የዘረዘርናቸው ችግሮች በሙሉ እንደ አካል እንደአስፈጻሚ እኛ እየመራን የተፈጸሙ ናቸው። እኚህ ጉዳዮች ከልብ ወደውስጥ ተቀብለን ኃላፊነት መውሰድ አለብን። ማንኛውም ተራማጅ አመራር እንደዚህ ዓይነት ነገሮች በሚፈጠሩበት ጊዜ በማያሻማ በማያወላዳ ሁኔታ የቡድንም የግልም ኃላፊነት መውሰድ የግድ ይላል የሚል ጽኑ እምነት አለን ብለዋል፡፡
የብአዴን ሊቀመንበርና የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው እንዳሉት፣እራሱ ስብሰባው ግምገማው ሲጀምር ፣ሀገራችን በምን ሁኔታ ላይ ነው ያለችው? ድርጅታችን በምን ሁኔታ ላይ ነው ያለው? ነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታ እና ከዚህ ለመውጣት ምንድነው የሚያስችለው የሚለውን አስቀምጧል። ችግሮችን በዝርዝር ነቅሶ በማውጣት ባለቤት ተቀምጧል። ይህንን እንደ ወሳኝ እርምጃ ወስደን ባለቤቱ ደግሞ ዋናው የላይኛው አመራር ሄድ ኳርተሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ራሱ እንደሆነ፣ለሌላው ጣቱን አልቀሰረም፣ለሌላ አላመላከተም።
በስራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ውስጥ እንኳን፣እንደየሀላፊነት ድርሻው በዛ ላይ የነበረው ሚና ሁሉም እዛ ያለ አመራር በግልጽ አስተማሪ በሆነ ሁኔታና በተቆርቋሪነት ይህን በደል፣ይህን አደጋ፣ይህን ችግር ለችግሩ ዕድሜ መግዛት እና ለዚህ ሁኔታ መፈጠር ተጠያቂ ነኝ የሚለውን ነገር አስቀምጧል።ለዚህ ነው ስራ አስፈጻሚው ኮሚቴው ለዚህ ችግር ዋናው ባለቤት እኔነኝ የሚለው።
በዚህ ደረጃ ባለቤትነት ሲወሰድ አሰራርና ስርዓትን ጠብቆ ያኛው ደግሞ ከየብሄራዊ ድርጅቶች ጋር እየተሳሰረ ዝርዝር ግምገማዎች ሲካሄዱ የበለጠ ሁሉም በየድርሻው የሚወስደው ሀላፊነት የሚወስደው ተጠያቂነትና ትምህርት ይኖራል። እዚህ ላይ ትልቁ ቁምነገር ምንድነው? ችግር ሲለይ ሲባል ከግለሰቡ ጋር አጣብቆ አንድን አካል በማውጣት በማውረድ አይደለም።
መጀመሪያ የስርዓት ችግር መለየት ነው። ያ ሰፊ ርብርብ ተደርጎ ተለይቷል። የስርዓት ችግር ሲለይ ለስርዓት ችግር መፈጠር ተዋናዩ የድርሻውን እንዲወስድ ማለት ነው። ሥራ አስፈጻሚው ያንን በግልጽ አስቀምጧል። በዚህ ላይ የተመሰረተ እንደ ቡድን ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴው ቢወስድም፣ መውሰድም ስላለበት እንዲሁ በአጠቃላይ አነጋገር የሚቀመጥ ብቻ ሳይሆን በዝርዝር ደግሞ ቀደም ባልኩት አሰራሮች ሁሉም ትምህርት የሚወስድበትና ያ ተጠያቂነት የሚቀመጥበት ይሆናል የሚለው ነገር ግልጽ መሆን አለበት። ይሄ ወሳኝ እርምጃ ነው።
የወሳኝ እርምጃው ማሳረጊያ በስርዓት ደረጃ የተለየውን ችግር የችግሩ ባለቤት እኔ ነኝ ብሎ እጅግ አስተማሪ በሆነ ሁኔታ ተቆርቁሮ እንደ ቡድን ችግሩን የተቀበለው አካል የለየውን ችግር ለመፍታት ያስችለኛል ባለው መንገድ ምንም ሳያወላዳ ተጨባጭ መፍትሄና ትግበራ ውስጥ መግባት ነው።የተለያየ ምክንያት በመደርደር አይሆንም። ውሳኔና ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚጠበቀው ጉዳይ ይሄ ነው። በዚህ ማዕቀፍ ከታየ ወሳኝ እርምጃው እስከውጤቱ ድረስ ተያይዞ ፍሰቱ መወሰድ አለበት።የመጀመሪያው ምዕራፍ ግን ለዛ ደረጃ የሚመጥን፣እራሱን ወደውስጡ የተመለከተ እርምጃ ስለሆነ በዛ ደረጃ ቢታይ መልካም ነው።
ማን አሸነፈ? የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ አቶ ደመቀ እንዳብራሩት ፤ ተሸናፊ የለም። ሁሉም ችግሮችን ነቅሰው ባወጡበት፣ሚናቸውን በለዩበት፣በዚህ ደረጃ ችግር ሲደርስ የኔ ሚና ምን መሆን ሲገባው፣ምን አምልጦኛል የሚለውን አስተማሪ ነገር በማየት የየብሄራዊ ድርጅቶቹ አመራር የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ እንደ አካል የወሰደው ትምህርትና በችግሮቹ ላይ የፈጠረው ተግባቦትና መፍትሄዎቹን ማስቀመጥ ነው። አንዱ የመጀመሪያው የአሸናፊነት እርምጃ ነው። አሸናፊነት በዚህ አይቆምም።ይህ አሸናፊነት ደግሞ የሚረጋገጠው በዚሁ አግባብ ተጨባጭ የሆኑ ውጤቶች በተፈጠረው የአስተሳሰብ አንድነት ለተግባር አንድነቱ መሰረት ተጥሏል። በዛ መሰረት ላይ ተመስርቶ አፋጣኝ ለውጥና ምላሽ ህብረተሰቡ የሚጠብቀው ንቅናቄ በተግባር በማረጋገጥ ነው።
ይሄ አሸናፊነት በኢህአዴግ ደረጃ እንደ አካል አረጋግጦ ወጥቷል። ይሄ አሸናፊነት ወደ ብሄራዊ ድርጅቶች ዘለግ ብሎ እንዲወርድ ይጠበቃል። ብሄራዊ ድርጅቶቹም በዝርዝር ከዚህ በፊት በጀመሩት ላይ ተመስርቶ አሁን ከቆምንበትና አሁን ከምናስቀምጠው አተያይ ጋር የተያያዘ ብሄራዊ ድርጅቶቹን ሊለውጥና የበለጠ አቅም ሆኖ ሊያስኬድ የሚችል ግምገማዎችን ማየት ይኖርባቸዋል። በዛ ደረጃ አይተው ፣በብሄራዊ ደረጃና እንደ ሀገር በሚያገናኛቸው መስተጋብር ቆጥረው ለይተው የሚያስቀምጡበት መፍትሄና የአስተሳሰብ አንድነት አንድ የአሸናፊነት እርምጃ ይሆናል። ይህ ተያይዞ ከላይ እስከታች እንደ ግንባርም እንደ ብሄራዊ ድርጅቶች የሚደረገው ንቅናቄ የተሟላውን አሸናፊነት ያረጋግጣል። በዚህ አተያይ ነው የሚወሰደው ከዚህ እላፊ የተለያዩ የሚባሉ ነገሮች ቁምነገር አላቸው ተብለው ሊወሰዱ የሚችሉ አይደሉም።
ኢህአዴግ ከችግሩ ሊወጣ ይችላል? በሚለው ጥያቄ ላይም አቶ ደመቀ ማብራሪያ ሰጥተዋል። እውነት ነው ህዝቡ በዚህ ደረጃ ቢሰጋ ፣ቢጠራጠር የሚገርም አይደለም። የተጀመረ የለውጥ ጉዞ አለ።ድህነትንና ኋላ ቀርነትን የመለወጥ፣ጠንካራ ሀገር የመገንባት ፣ብልጽግናን የማረጋገጥ ጅምር አለ፡፡ ይህን የሚፈታተን አካሄድ ሁሉ ዋጋው ከባድ ነው። በስራው ፍጥነት መፍጠን በሚገባን ሁሉ አቀፍ ጉዞ ማረጋገጥ በሚገባን ያለው ጉድለት እንዳለ ሆኖ አሁን አሁን ደግሞ ከግጭት ጋር እየተያያዙ ሰላምና ደህንነቱን የሚያደፈርሱ ፣ስጋት ውስጥ የሚጥሉ፣ጉዳዮች ሲደማመሩበት ሌሎች ሌሎች ችግሮች እዚህ ጋር ሲሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግር ዕድሜ እየገዛ በዛ ደረጃ ሲመጣ እና ሌሎች ችግሮች ሲሰፉ ለምን አይጠረጥርም? ኢህአዴግ እንዴት ነው ከዚህ አኳያ የሚታየው? በዘረዘርነው ችግር ልንጠረጠር አይገባም? የሚለውን ነገር ቢጠረጥር አይገርምም።
ኢህአዴግ ሁሌም ለአንድ ጉዳይ መጀመሪያ በውስጡ እራሱን ይፈልጋል። በውስጡ ያለውን ችግር ያንኳኳል።ያንን ደፍሮ ይመለከታል። የእሱን የቤት ሥራ ከሰራ በኋላ ሌሎች ለዚህ መፍትሄ ሆነው እንዲቆሙ ሁኔታዎችን ያመቻቻል። በኢህአዴግ ውስጥ ብቻ የሚሰፈር የሚሰራ ሥራ የትም አያደርስም። መስተጋብሩ ወደ ህዝብና ወደ ለውጥ ይሸጋገራል። ኢህአዴግ ያ ጸጋው ራሱን ዋንኛ ተጠያቂና የችግር ባለቤት አድርጎ ማየቱ ያ ባህርይውና ያ እርሾው ገመዱ እነዛ መርሆዎቹን አለቀቀም ኢህአዴግ። እነዛ በተለያየ ችግር ጫና ደርሶባቸው እየተፋዘዙ ግን ደግሞ ቆም ብሎ ወደዚህ ግምገማና ወደዚህ ሁኔታ በመግባት እነዛ ጸጋዎቹን መሰረት አድርጎ እራሱን ጠይቆ ባለቤት ሆኖ መፍትሄዎቹን ይዞ ለሁሉም ተዘጋጅቷል ማለት ነው።
በዚህ ደረጃ ከተመጣ ይሄንን ይዞ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባት ነው፡፡ ብዙ መስቀለኛ መንገዶችን እየፈታ የመጣ ድርጅት የተለያዩ ፈታኝ ሁኔታዎችን እየፈታ የመጣ ድርጅት አሁንም በዚህ ምዕራፍ ላይ ተፈትኗል፡፡ በችግር አፈታት ደረጃ አንዱ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ወደመተማመንና የአስተሳሰብ አንድነት ደርሷል፡፡ በዚህ ደረጃ የመጣው እንደዋዛ አይደለም፡፡ ለሆነ ፍጆቻ አይደለም፤ አገርን አስቀድሞ በማየት፣ ከራሱ በላይ ህዝብንና አገርን በማየት ነው፡፡ ይሄንን ወደ ተግባር መንዝሮ የህዝብ እርካታን ለማረጋገጥ ከዚህ ስጋት ለመውጣት በግምገማ ላይ በዝርዝር በለያቸው ችግሮች፤ በዚያ ላይ ተለይተው በተቀመጡ ችግሮች በፍጥነት ወደ ተግባር መግባትና ምላሽ መስጠትም ይጠይቃል፡፡
ለዚህ ኢህአዴግ ዝግጁ ነው፡፡ እንደ አካልና እንደ ግለሰብ ከፍተኛ መቆርቆር ወስዶ ቀጣይ የሚኖሩ መድረኮችን ተደማሪ አቅም አድርጎ ይሄን ሊለውጥ ይችላል፡፡ ይሄን ለመለወጥ የሁሉም አቅሞች፣ የህብረተሰቡ ተሳትፎ፣ የህብረተሰቡ ጠያቂነት፣ የህብረተሰቡ ባለቤትነት በተለያዩ አደረጃጀቶች፤ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪል ማህበራት፣ የምሁራን፣ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለመፍትሄው የምንገነባው የጋራ አገራችንን ስለሆነ የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ በግልጽ ያስቀመጠው ነገር አለ፤ ያንን ተመስርተን ልንለውጠው እንችላለን፡፡ ትክክለኛ መንገድ ላይ ነው ያለነው፡፡ ለዚያም ኢህአዴግ እሴቶቹንና መርሆዎቹን ጠብቆ እውን ለማድረግ ተዘጋጅቷል፡፡
የሚወሰደውን ሃላፊነት በተመለከተ የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን እንዳሉት ዋናው ነገር አገር ሊበትኑና ህዝብን ወደ ከፍተኛ ትርምስ ሊያስገቡ የሚችሉ ችግሮች መፍትሄ ተቀምጧል፤ በአገራችን እየታየ ያለው ችግር የመጨረሻውን መፍትሄ አግኝቷል የሚለው ነው ? ችግሮቹ በጣም የከፉ ናቸው፡፡ እየተባባሱ የሚሄዱ ናቸው፡፡ ቶሎ ካላስተካከልነው ወደ ትልቅ ጉዳት ያደርሰናል፡፡ ስለዚህ ይሄ መቀየር አለበት በማለት፤ ችግሩ ፖለቲካዊ ስለሆነ መፍትሄውም ፖለቲካዊ መሆኑ ተነስቷል ብለዋል፡፡ ስለሆነም ፖለቲካዊ ግምገማው ቅድሚያ ይሰጠዋል ከሁሉም በላይ፡፡ ፖለቲካዊ መፍትሄ ካልተቀመጠ ሰው ቢቀያየር መፍትሄ አይመጣም፡፡ ስለዚህ ዋናው ችግር መጀመሪያ ተቆጥሮ ተለይቶ መቀመጥ፣ ለዚያ ደግሞ መፍትሄ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡
መፍትሄ ለማስቀመጥ በችግሮቹ ላይ መተማመን ያስፈልጋል፡፡ ችግሮችን ማስቀመጥ ራሱ ግማሽ መፍትሄ ነው ይባላል፡፡ ሰው ከዚያ በኋላ ነው የሚመጣው፡፡ ይሄ ደግሞ እንዳልነው የአመራር ነው፡፡ እንደ አካል የቡድን የተባለው ትልቅ ውሳኔ ነው፡፡ እንደ አካል ነው ችግር ያለው ተብሏል፡፡
መጨረሻውስ ተግባር ላይ ነው የሚታየው፡፡ ስለዚህ በዚህ በመድረክ ደረጃ በጣም ታሪካዊ ነበር፡፡ እንደተለመደው እንዳይሆን ነበር ያልነው እንደተለመደው አላደረግነውም፡፡ መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ሥራ ነው የተሰራው፡፡ ውጤት አግኝተንበታል፡፡ በአመራር ላይ የነበሩ ችግሮችን በመሰረቱ ፈትተናል፡፡ አብሮ የመስራት ችግር ነበር፡፡ የላላ ግንኙነት ነበር፡፡ ይሄ ተጠግኗል፡፡ ወደ መስመር ተገብቷል፡፡ ስለዚህ በአመራር ላይ የነበረው ትልቁ ችግር መፍትሄ አግኝቷል፡፡ በቀጣይ ትግል ደግሞ የበለጠ ይጠናከራል፡፡
የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል አሸናፊው ማነው የሚለውን ጥያቄ በተመለከተ እንዳብራሩት በመሰረቱ አሸናፊው አስተሳሰባችን ነው፡፡ የኢህአዴግ ዋናው የአስተሳሰብ መስመር ህዝባዊነት ነው፡፡ መሸራረፍ እና ለግል ጥቅም ማሰብ ነበር፡፡ ቡድንተኝነትና መተሳሰር ነበር፡፡ ይህን ትስስር ለመበጣጠስ ጥረት ተድርጓል፡፡ ስለዚህ ወደ ረድፍ ገብቷል፡፡ አሰላለፉን አስተካክሏል፡፡ ግምገማው በጣም ትልቅ ውጤት ተገኝቶበታል፡፡ ሁሉም አሸናፊ ሆኖ ወጥቷል የተባለው ለዚህም ነው ፡፡ አሸናፊው መስመር ነው፡፡ ተሸራርፈው እና ተዳክመው የነበሩ እሴቶቻችን ተመልሰው መጥተው መድመቅ ጀምረዋል ብለዋል፡፡
የኢህአዴግ ልምድም ይሄው ነው፡፡ ብዙ ችግሮች ሊያጋጥሙት ይችላሉ፡፡ ልምዱ ምንድን መማር ነው፡፡ ራሱን ከፈተሸ ይወጣል፡፡ ስለዚህ አሁን የጀመርነው የዚህ አመላካች ነው ፡፡ ተግባር ይቀጥላል፡፡ እንደተገለጸው በርካታ መድረኮችም አሉ፡፡ የመጀመሪያው ሥራ ሰበብ አስባብ የማምጣት ሳይሆን ራስን መፈተሽ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂ እኔ ነኝ ብሎ ኃላፊነቱን እወስዳዋለሁ እያለ፡፡
ይህ ማለት ግን ሌሎች እንቅፋት አልተፈጠሩም ማለት አይደለም፡፡ የውጭም እንቅፋቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ችግሩ ግን እነሱ አይደሉም ፣እነሱን ስርዓት ማስያዝ የነበረብኝ እኔ ነኝ፤ ጥፋቱ የኔ ነው፤ያልመለስኩት ብዙ ጥያቄ ስላለ ዋናው ተጠያቂ እኔ ነኝ እያለ ነው፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያው ይሄ ነበርና ድርጅቱ ወስኗል፤ ይሄ አመራር አሰላለፉን አስተካክሏል ፡፡ ወደ ቦታው እየገባ ነው፡፡
ኢህአዴግ ህዝብን ነው የማገለግለው ብሏል፡፡ ይህም በጣም ትልቅ ውሳኔ ነው፡፡ ችግሩን አብጠርጥሮ አይቶታል፡፡ይህ ጉዳይ ከፍተኛ አመራሩ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሊነጋገርበት የሚችል አጀንዳ መሆኑን እናውቀዋለን፡፡
በእኛ አመራር ስንት ሰው እኮ ሞቷል፤ተፈናቅሏል ፡፡ ከዚህ የማይማር ምን ይባላል፡፡ ስለዚህ ችግሩ በጣም ከባድ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ይሄ መታየቱ በራሱ ያሳስባል፡፡ ስለዚህ ሁኔታውን ቀለል አርገን መውሰድ አይኖርብንም፡፡ በጣም ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን መወሰን ያስፈልጋል፡፡ ሀላፊነት መውሰድ የግድ ነው፡፡
ይህን ችግር ለመፍታት ልምዱ ፣መስመሩ እና ህዝባዊነቱ ይጠቅማል፡፡ አሁን እየታደሰ ያለውም ይሄው ነው፡፡ እራሳችን እናድስ ያልነውም ለዚህ ነው፡፡ በጥልቀት መታደስ ማለትም ይሄው ነው፡፡ ተደጋግሞ እንደተገለ ጸው፤ብቻችንን እንሰራዋለን ማለት ግን አይደለም፡፡ በድርጅትም ብዙ ሥራ አለ፡፡ ከህዝብ ጋርም ብዙ ሥራ አለ፡፡ ቀጣይ ስራዎች አሉ፡፡ ግን እየሰራን እንታደሳለን፡፡ እየታደስን እንሰራለን ፡፡
ስለዚህ ይሄ ብዙ መማማል የሚያስፈልገው ነገር አይደለም፡፡ ለውጡ ራሱ መጥቷል፡፡ ይህን አሁን በመድረኩ ኢህአዴግ አሳይቷል፡፡ ይሄን መድረክ ማየት ራሱ በቂ ነው፡፡ ከባለፈው የተሻለ ምን ያህል የራሱን ኃላፊነት ወስዷል፤ ምን ያህል ራሱን ተጠያቂ አድርጓል፤ ይሄኛው የተለየ ነው፡፡ ወደ ኋላ ተመልሰን ማየት እንችላለን፡፡ ይሄ አዲስ ምዕራፍ እና ታሪክ ስለሆነ የተለየ ነው፡፡
እንዳልነው በዚህ መድረክ ብቻ ልንቋጨው አንችልም፡፡ በቀጣይ ይሄ ጅምር በራሳችንም፣ ከህዝቡ ጋርም ሆነን መጠናከር አለበት፡፡ አጀማመሩ የሚባለውን ችግር ለመፍታት ምቹ ሁኔታ፣ ጥሩ መነሳሳት፣ ቁጭትም ያለበት እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
የኦህዴድ ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው የሚወሰደውን ሃላፊነት በተመለከተ እንዳብራሩት ይህ ሥራ አስፈጸሚ ገዥውን ፓርቲ ፖለቲካውን በመምራቱም፣ የመንግስቱን ሥራ በመምራቱም በኩል ትልቅ ኃላፊነት ያለበት አካል እንደመሆኑ መጠን ለዚህ ሁሉ ችግር ባለቤቱ እኔ ነኝ ሲል እነዚህን ነገሮች ከግምት በማስገባት ነው ብለዋል፡፡ ስለዚህ ተጠያቂ ነው፡፡ ቀጣይ ደግሞ እያንዳንዳችን በግል ኃላፊነቶች አሉብን፡፡ በኃላፊነታችን ልክ እና በጥፋታችን ልክ የምንጠየቅበት አግባብ ይኖራል፡፡
በዚህ ግምገማ ያሸነፈው ፓርቲ ማን ነው የሚለው ቀደም ሲልም ወደዚህ ግምገማ የገባነው ለውድድር አይደለም ብለዋል፡፡ አንዱን ሻምፒዮና ለማድረግ አይደለም፡፡ አንዱ ሻምፒዮና ሆኜ ወጣሁ ቢልም የሚሸለመው ሜዳሊያ አይኖርም፡፡ ነገር ግን በግልጽ መታየት ያለበት፤ ወደዚህ ግምገማ ስንገባ በተለያየ ስሜት ውስጥ ሆነን ነው፡፡
የቆምንለትና የታገልንለት ህዝብ አለ፡፡ እየሰራንም፤ እየወደቅንም እየተነሳንም ብዙ ችግር አጋጥሞናል፡፡ ሀገሪቷ በቀውስ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ሀገርን ህዝብን እንደምንመራ ሁሉ ሁላችንም ኃላፊነት እንደሚሰማው አመራር ሆነን ወደዚህ ግምገማ የገባነው ይህን ሁሉ ስሜት ይዘን ነው፡፡
እኔ የግምገማውን ሂደት በሙሉ በቀጥታ ስርጭት ለህዝቡ በለቀቅን ኖሮ እላለሁ፡፡ መቋሰሉ፣ የችግሩ ጥልቀት ምን ያህል እያንዳንዳችንን እንደተሰማን ህዝቡ ቢያይ ኖሮ ፍርዱን መስጠት በቻለ ነበር እላለሁ፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው አንዱን ለማጀገን እና ሌላውን ሎሌ ለማድረግ አይደለም፡፡ በየዕለቱ ህይወት እየጠፋ ነው፤በእጃችን ደም እየፈሰሰ ነው፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከህጻን እስከ አዛውንት ከቀዬያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ሀገሪቷ ቀውስ ውስጥ ወደዚህ ግምገማ የገባነው የግለሰብ ክብር እና ስልጣን ገደል ይግባ፤ ከሀገር አይበልጥም ብለን ነው፡፡ የሁላችንም ስልጣን እና ክብር ከሀገር በታች ነው፡፡ በዚያ ደረጃ እናያለን የሚል ስሜት ይዘን ነው ወደ ግምገማው ገብተን ስናይ የቆየነው፡፡
ሀገራችንን እናድን፡፡ አደገኛ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ሁለት ምርጫ ነው ያለን፤ የመፍረስ ወይም የመዳን፡፡ በዚህ መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆመን አሸናፊን እና ተሸናፊን የምናማርጥበት ሁኔታ የለም፡፡ ያለውን ሁኔታ በግልጽ ተነጋግረን የምንነቅፈው በግልጽ እንዲነቀፍ፤ የምናስተካክለው በግልጽ እንዲስተካከል ማድረግ ነበረብን፡፡ በዚህ ረገድ የሚገባንን አድርገናል ብለን እናስባለን፡፡
ማናችንም ሳንሸማቀቅ ማድረግ ያለብንን፤ እንደ ኦህዴድ በዚህ ውስጥ ማድረግ የሚገባንን ትግል ሁሉ በቁርጠኝነት አድርገናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ደኢህዴን ማድረግ የሚገባውን ትግል አድርጓል ብዬ አምናለሁ፡፤ ብአዴን ማድረግ የሚገባውን ትግል አድርጓል፤ ህወሃትም እንደዚሁ፡፡ ቀጥለን ደግሞ መስራት ይኖርብናል፡ በተግባር ለህዝቡ ማሳየት አለብን፡፡ ይህን ማድረጋችንን ያየነው እኛ ነን እንጂ ህዝቡ አላየም፡፡ ህዝቡ የሚያየው ከተግባራችን ነው፤ በውጤታችን ማሳየት አለብን፡፡ ስለዚህ አንዱን የማንገስ እና አንዱን የመጣል ጉዳይ ውስጥ አልቆየንም፡፡ ይህን የሚፈቅድ ሁኔታ ውስጥ አይደለም፡፡ በእርግጥ የተሸነፉ አካላት ግን አሉ፡፡ መድረካችን ላይ ቢሆንም እውነት አሸንፏል፤ ውሸት ደግሞ ተሸንፏል፡፡ ቡድን እና ኔት ወርክ እያደራጁ ስልጣናቸውን መደላድል አድርገው ለሀገሪቱ ሳይሆን ለራሳቸው ጥቅም የቆሙ ተሸንፈዋል፤ ቡድንን ፈጥረው የሚለፋውን እየገፉ ከዚህ የበለጠ ለመጠንከር የፈለጉ ቡድኖች በግልጽም በዚህ መድረክ ላይ ተሸንፈዋል፡፡
ጉዳቱ የጋራችን ስለሆነ ይህን ማድረግ የሁላችንም ግዴታ ነው፡፡ በስሜት የሚደረጉ ነገሮች ውጤታቸው መልካም አይሆንም፡፡ ሁሉም ነገር በምክክርና በንግግር ሲሆን ውጤቱ ያምራል፡፡
የሃገራችንን የቅርብ ጊዜ ታሪክ መለስ ብለን ማየቱም በጣም ያስፈልጋል፡፡ በኢሃፓ ዘመን በዚህ ሀገር ውስጥ ስንት ጭንቅላት ጠፍቷል፡፡ አንድ ትውልድ ብቻ ሳይሆን የተሻለ ትውልድ በከንቱ ጠፍቷል፡፡ ይህ ጥቁር ጠባሳ በሃገራችን እንዲደገም አንፈልግም፡፡ መግባባትም ሆነ መለያየት በንግግርና በምክክር ብቻ መፈጸም ያለበት፡፡ በጉልበትና በጉልበት የሚሆነን ነገር አያምርም፡፡ ውጤቱንም ኪሳራውንም አይተነዋል፡፡ ያ ታሪክ መደገም የለበትም፡፡ ሁሉንም ነገር ለመቀበልም ለመቃወምም ንግግርና ንግግር መተቻችት መከራከር ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው ወደዚያ እንዳንመለስ ዴሞክራሲውን እናስፋ፤ ፣ሰው የሚናገርበትን የሚደመጥበትን ሃሳቡን የሚያንሸራሽርበትን ዕድል እናስፋ የምንለው፡፡ ሃገራችንን ለማዳን ሁላችንም በትእግስትና ሃላፊነት በተሞላበት መንፈስ መስራት ይኖርብናል፤ይህ የሁላችንም ሃላፊነት መሆኑን በዚህ አጋጣሚ እገልጻለሁ፡፡
የአራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች አመራሮች በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የሰጡትን ማብራሪያ በቀጣይ እትማችን ይዘን እንቀርባለን፡፡

 

Published in ፖለቲካ
Thursday, 11 January 2018 20:01

ሰባ ዓመት በስኬት

ከዕድሜ ባሻገር በሥራ ቢመዘን ‹‹አንጋፋ›› የሚለው ቃል በሚገባ ይገልፀዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ሰባኛ ዓመት የልደት ሻማውን ሲያበራ በሦስት የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ ስኬትን ጠብቆ የአገር ምልክት መሆኑን አስመስክሯል፡፡ ከአገር አልፎ የጥቁር ህዝቦች ኩራት ሆኖ የዘለቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬም አፍሪካን ከተቀረው ዓለም ማስተሳሰሩን ቀጥሏል፡፡ በቅርቡ ደግሞ ለአካባቢ ጥበቃ የተቆርቋሪነት መርህ አንግቦ የተቋሙን አሰራር ወረቀት አልባ የማድረግ ጥረቱን በብዙ መንገድ ማሳካቱን ተያይዞታል፡፡ ይሄም ከቢሮ ውስጥ ሥራ እስከ ደንበኞች የትኬት አቆራረጥ ድረስ የተሳሰረ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡
አየር መንገዱ የዚህ ጥረቱ አካል የሆነውን አዲስ አገልግሎት በቅርቡ አስተዋውቋል፡፡ በሞባይል አፕሊኬሽን የተቋሙ ደንበኞች ከቅርንጫፍ ቅርንጫፍ መጓጓዝ ሳይጠበቅባቸው ባሉበት ስፍራ ሆነው ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ነው፡፡ ሰሞኑን በተደረገ መርሐ ግብር ላይ ቴክኖሎጂውን ያስተዋወቁት የአየር መንገዱ የአይቲ ክፍል ባለሙያዎች በስራቸው ከፍተኛ ምስጋና ተችሯቸዋል፡፡ የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም አፕሊኬሽኑን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር፤ ደንበኞች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ አየር መንገድ የተቋሙን አሰራር ይበልጥ በቴክኖሎጂ ለማዘመን ጥረት እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡
አየር መንገዱ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ሦስት መንግሥታት ፖሊሲ ውስጥ ቢያልፍም ከስኬት ወደኋላ የጎተተው አጋጣሚ እንብዛም አልነበረም፡፡ ከሰባ ዓመት በላይ በአህጉሩ የአየር መንገዶች ታሪክ የስኬት ጉዞ ለመዝለቁ የመላው ሠራተኛ ትጋት ውጤት መሆኑን የገለጹት አቶ ተወልደ፤ ተቋሙ አሁንም ብዙ ውድድር በበዛበት ዘርፍ ትርፋማነቱን እንዳስጠበቀ ለመዝለቅ ያስቻለው ይሄው ትጋቱ ነው፡፡ ከተቋሙ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ያለፈው ዓመት እ.አ.አ 2017 ለአየር መንገዱ ታሪካዊ የስኬት ዘመን በመሆን አልፏል፡፡ የበረራ መዳረሻ መስመሮች ከማበራከት ባሻገር ተቋሙ ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ባልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ የተረጋጋ ጉዞ ላይ መገኘት ማለት ይሄ ነው፡፡
ሥራ አስፈፃሚው አቶ ተወልደ ‹‹ባለፉት ሰባት ዓመታት አየር መንገዱ ባስቀመጠው ስትራቴጂያዊ ፍኖተ ካርታ አማካኝነት በጣም ተለዋዋጭ፣ የማይጨበጥ፣ ውስብስብና አሻሚ በሆነው ዘርፍ ውስጥ ዘላቂነት ያለው ፈጣንና ትርፋማ ጉዞን ማድረግ ችለናል›› በማለት፤ ተቋሙ ባስቀመጠው ራዕይ 2025 መሰረት እ.አ.አ 2017 ብቻ 12 አዳዲስ መዳረሻዎች በረራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ዘመናዊና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀሙ ማጓጓዣና ዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች በመጠቀም አገልግሎቱን በማሳደግ ላይ ይገኛል፡፡ በተያዘው የአውሮፓውያን ዓመትም ይሄንኑ ጅምር በማጠናከር በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱ እንደሚቀጥል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ይገልጻሉ፡፡
የአየር መንገዱን ትርፋማነት በተመለከተ አምና ከአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ ተለዋዋጭነት ጋር በተያያዘ የዘንድሮውን ግማሽ ዓመት ትርፍ መገመት ባይቻልም ባለፈው ዓመት ግን 260 ሚሊዮን ዶላር ትርፍ መገኘቱ ተጠቅሷል፡፡ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያን በተመለከተም፤ ለተጓዦች የጉዞ አገልግሎት ከመስጠት በተጓዳኝ በአውሮፕላን ጥገና ያለውን ልምድ ይበልጥ ለማሳደግ ከተለያዩ ጥገናዎች በተጨማሪ የሦስት ትላልቅ ጋራጆች ግንባታ አከናውኗል፡፡ በዕቃ መጫኛ አገልግሎቱም በግዝፈቱ ከአፍሪካ የቀዳሚነት ደረጃ የሚያሰጠውና ከአምስተርዳሙ ስቺምፖል እንዲሁም ከሲንጋፖርና ሆንግ ኮንግ ጋር ተወዳዳሪ የሆነ ነው፡፡
በሌላ በኩል በተያዘው ዓመት ተጠናቆ አገልግሎት እንደሚጀምር የሚጠበቀው ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል የአየር መንገዱን አገልግሎት በከፍተኛ ሁኔታ የሚሳድገው ይሆናል፡፡ በከተማዋ ተጨማሪ ግዙፍ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከመያዙም ባሻገር በአህጉሩ የመጀመሪያው የሆነ ትልቅ የቻይናውያን ሬስቶራንትም እንደሚኖረውም ታውቋል፡፡ በማሰልጠኛም ዘርፍ የተሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ጉዞውን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
አየር መንገዱ ባስተዋወቀው የሞባይል አፕሊኬሽን የቲኬትና ተጓዳኝ አገልግሎቶች ማስተዋወቂያ ላይ የአየር መንገዱ የረጅም ጊዜ ደንበኞችና የተለያዩ ተቋማት ተወካዮች ታድመዋል፡፡ እንዲህ ያለው መድረክ በተለይም በስኬቱ ተጠቃሽ በሆነ ተቋም በኩል ሲደገስ ለልምድ ልውውጥ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡ በመድረኩ የታደሙ አካላትም ይሄን የሚያንፀባርቁ ሃሳቦች አንሸራሽረዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የአየር መንገድ ውድድሩ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ከመጠየቅ አንስቶ በዘርፉ እስከሚስተዋሉ አንኳር ማነቆዎች ላይ እስከመወያየት የደረሰ የሃሳብ ማንሸራሸሪያ አጋጣሚን ፈጥሮ ነበር፡፡
ስኬትን በተመለከተ ከሰባ ዓመቱ ታሪክ ይልቅ ያለፈውን ሰባት ዓመት ሁኔታ በማስቀደም ንግግራቸውን የሚጀምሩት ዋና ስራ አስፈጻሚው ‹‹ያለፉት ሰባት ዓመታት በአፍሪካ አየር መንገዶች ታሪክ በጣም ፈተና የበዛባቸው ዓመታት ነበሩ›› ይላሉ፡፡ በተለይም የኢቦላ ወረርሽኝ፣ እየተስፋፋ የመጣው የሽብርተኞች እንቅስቃሴ፣ የእርስ በእርስ ጦርነት፣ በአንዳንድ አገሮች የተስተዋለው የኢኮኖሚ ቀውስ እንዲሁም ሌሎች ምጣኔ ሀብታዊ ማሻሻያዎች አጠቃላይ ዘርፉን በፈተና አንቀው የያዙት ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ጫናዎች ያስከተሏቸውን ቀውሶች በመቋቋም በዕድገት ጉዞ የቀጠለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ አዳዲስ መዳረሻዎችን በአዳዲስ መጓጓዣዎች ሲያደርግ ነበር፡፡
ታዲያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች በተለየ ለምን በስኬት ዘለቀ? ይሄን ጥያቄ ያነሱት የፌር ፋክስ አፍሪካ ፈንድ ሊቀመንበር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ፤ ለመሆኑ ተቋሙ ከሰባ ዓመት በላይ ከዘለቀው ስኬቱ ባሻገር ያለው ሚስጥር ምን ይሆን? ሲሉ ጥያቄያቸውን ያጠናክራሉ፡፡ የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ፤ በስኬት ለመዝለቁ በርካታ ሚስጥሮች መኖራቸውን ያብራራሉ፡፡ እነዚህ ሚስጥሮች ከተቋሙ የላይኛው አስተዳደር ጀምሮ መላውን የአየር መንገዱ ሰራተኞች ዋጋ የሚያሰጥ መሆኑን በማብራራት፡ አንድ ተቋም ‹‹መሪውን ይመስላል›› እንዲሉ የመጀመሪያው የስኬት ሚስጥር አመራሩ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ የተቋሙ ሠራተኞች በሙሉ ከታችኛው እስከ ከፍተኛው አመራር ድረስ ያካበቱት ሰፊ ልምድና በውስጣቸው ያለው ቁርጠኝነትን በጉልህ የሚጠቅሱት አቶ ተወልደ፤ ይሄ ልምድና ቁርጠኝነት ተቋሙ ያለፈባቸውን ፈተናዎች በጥንካሬ እንዲሻገር ምክንያት መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች ደመወዝ ከሌሎች አገራት የአየር መንገድ ሠራተኞች ደመወዝ ጋር የሚነፃፀር አይደለም›› የሚሉት አቶ ተወልደ፤ ሰራተኞች ከገንዘብ ይልቅ ለብሔራዊ ተልዕኮ ቁርጠኛ ሆነው መስራታቸው የስኬት ሌላኛው ሚስጥር ያደርጉታል፡፡
‹‹አየር መንገዱ ሕይወታችን ነው›› ሲሉ የአየር መንገዱን ሠራተኞች በመወከል የገለጹት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ ከ13ሺ በላይ የሆነው የአየር መንገዱ ሠራተኛ ያለውን ብቃት በሙሉ ለቆመለት ዓላማና ተልዕኮ በሕብረት መጓዙ ለስኬት እንዳበቃው ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል ተቋሙ የሚመራበት አስተዳደር ለሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ምሣሌ ያደርገዋል ይላሉ፡፡ ለአብነትም የአየር መንገዱ ባለቤት መንግሥት ቢሆንም የአየር መንገዱ የዕለት ተዕለት ሥራ የሚከናወነው ግን በባለሙያዎች ብቻ ነው፡፡ ‹‹በአየር መንገድ ቢዝነስ ይሄ ተሞክሮ በጣም ጥቂት በሚባሉት ዘንድ የሚተገበር ነው›› የሚሉት አቶ ተወልደ፤ ተሞክሮውን በአግባቡ ለተጠቀመበት በግል ኢንቨስትመንትም ውስጥ ባለቤትነትን ከአስተዳደር ነጥሎ መመልከት ለስኬት ያበቃል፡፡ ምክንያቱም በዓላማና ድርሻ መካከል ያለውን ልዩነት በአግባቡ መረዳት ጠቃሚ ጉዳይ ይሆናል፡፡
እንደ አህጉር በአፍሪካ የተለያዩ አገራት የመንግሥት አየር መንገዶች በአስተዳደራቸው ውስብስብ ችግር ምክንያት ብዙ ፈተና እንደገጠማቸው ያስታውሳሉ፡፡ አስራ አንድ አባል አገሮችን የሚያቅፈው ኤር አፍሪክ ጨምሮ የናይጄሪያ፣ የጋና፣ የዛምቢያ እንዲሁም የዚምባብዌ አየር መንገዶች ዛሬ ታሪክ ሆነው ለመቅረታቸው ምክንያቱም በመንግሥትና በተቋም አስተዳዳሪዎች መካከል ያለው የሚና ልዩነት በአግባቡ ባለመፈተሽ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ እነዚህ አየር መንገዶች በነበረባቸው የበዛ ጣልቃ ገብነት ምክንያት አስተዳደራቸውም እየተሽመደመደ ሊሄድ ችሏል፡፡
በአጠቃላይ አየር መንገዱ በርካታ ተጓዦችን ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ ሲያጓጉዝ አብራ የምትጓዘው አገር ነች፡፡ ኢትዮጵያን በመላው ዓለም በአምባሳደርነት የሚያስተዋውቀው አየር መንገዱ፤ በጥቁር የነፃነት ትግል ውስጥ ለበርካታ ፋኖዎች የብርታት ስንቅ ሆኖላቸዋል፡፡ ይሄ የአየር መንገዱ አለም አቀፋዊ ዝና በአገሪቱ ለሚገኙ በተለይም የአፈፃፀም ችግር ላለባቸው ተቋማት ምሳሌ ሊሆን ይገባል፡፡ በተለይም በሚሰጧቸው አገልግሎቶች በየጊዜው ሕዝብን የሚያማርሩ ተቋማት ጎራ ብለው ልምድ መቅሰም ይገባቸዋል፡፡ አየር መንገዱም ልምዱን ለማካፈል በሩን ይበልጥ መክፈት ይጠበቅበታል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

እስራኤል በሕገወጥ መንገድ በሀገሯ የሚኖሩ ብዙ ሺ አፍሪካውያን ስደተኞች ገንዘብ እየሰጠች ለማስወጣት ውሳኔ አሳልፋለች፡፡ ስደተኞቹ በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ካልወጡ ግን ከመጋቢት መጨረሻ በኋላ እንደምታስርም ሮይተርስ ዘግቦታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ በግልጽ በካቢኔ ስብሰባ ላይ የአፍሪካ ስደተኞችን የክፍያ ፕሮግራም አስመልክተው ሲናገሩ ስደተኞች ወደመጡበት ሀገር ወይም ወደ ሦስተኛ ሀገር እንዲሄዱ ይደረጋል ሲሉ በይፋ ለሕዝብ ተናግረዋል፡፡
እስራኤል በ2013 ከግብጽ ጋር በሚያገናኛት ድንበር ሕገወጥ ስደተኞች ወደግዛቷ ማለፍ እንዳይችሉ ማገጃ ገንብታ ጨርሳለች፡፡ ይህ የማገጃ መስመር በመሰራቱ እስራኤል ሙሉ በሙሉ ውጤታማ በሆነ መልኩ ወደሀገሯ በሕገወጥ መንገድ የሚገቡትን ስደተኞች ማስቆምና መግታት ችላለች፡፡ ማገጃው ከመሰራቱና ከመጠናቀቁ በፊት ሰልሳ ሺ ያህል ከአፍሪካ የፈለሱ ሕገወጥ ስደተኞች በግብጽ በኩል ያለውን በረሀ አቋርጠው ወደ እስራኤል ገብተዋል፡፡
ወደ እስራኤል የገቡት ብዛት ያላቸው ሕገወጥ ስደተኞች የመጡት ከኤርትራና ሱዳን ሲሆን ብዙዎች እንደሚሉት የተሰደዱት በአገራቸው ያለውን ጦርነትና ግድያ በመሸሽ እንዲሁም ከባድ በሆነ የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ነው፡፡ ሆኖም እስራኤል በኢኮኖሚ ስደተኝነት ነው ያስተናገደቻቸው፡፡ እስራኤል ይፋ ባደረገችው እቅድ መሰረት ለአፍሪካ ስደተኞች ሦስት ሺ500 ዶላር (2900 ፓውንድ) ክፍያ በመስጠት ወደሀገራቸው እንዲመለሱ ወይም ወደሦስተኛ ሀገር እንዲሄዱ እንዲሁም ነጻ የአየር መጓጓዣ ትኬት ከእስራኤል መንግስት ይሰጣቸዋል፡፡የሰብዓዊ መብት ቡድኖች ሦስተኛ ሀገር የተባሉት ሩዋንዳና ኡጋንዳ መሆናቸውን ለይተዋል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ቀደም ባሉት ግዜያት ወደ 20ሺ ሕገወጥ ስደተኞችን አስወጥተናል፤ አሁን ያለው ግዳጅ ቀሪዎቹን መሸኘት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የስደተኞች መስሪያ ቤት ባለስልጣን፤ እስራኤል ውስጥ በሕገወጥ የሚኖሩ 38 ሺ የሚደርሱ ስደተኞች እንዳሉ አስታውቀዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንድ ሺ420 የሚሆኑት በሁለት የእስር ማእከሎች እንደሚገኙ ከመጋቢት በፊት በፈቃዳቸው ሀገሪቱን ለሚለቁት አነስተኛ ክፍያ የሚሰጥ መሆኑን የገንዘቡ መጠን ጊዜው ሲጨምር እያነሰ እንደሚሄድ ሕገወጥ ስደተኞቹ በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ተጠቅመው እስራኤልን ለቀው የማይወጡ ከሆነ አስገዳጅ የማሰር እርምጃዎች የሚጀመሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አንዳንዶቹ ለጥቂት ዓመታት በእስራኤል በመኖር በጣም ዝቅተኛ ክፍያ ባላቸውና ብዙ እስራኤላውያን በማይፈልጓቸው ስራዎች ተሰማርተው ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡እስራኤል ከአጠቃላዩ አንድ በመቶ ለሚያንሱት ስደተኞች ጥገኝነት እንዲሰጣቸው ላመለከቱትና ከዓመት በላይ የቆየ ማመልከቻ ላላቸው ጥቂቶች ብቻ ጥገኝነት ሰጥታለች፡፡ እስራኤል የአፍሪካ ስደተኞችን የጥገኝነት ጥያቄ ሂደት ታዘገያለች ይህም በፖሊሲዋ ምክንያትና ጥያቄውን ሕጋዊ አድርጋ ባለመቀበል ነው ሲሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ይከሷታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ የስደተኞች በእስራኤል መገኘት ለእስራኤል ማሕበራዊ ትስስርና ለአይሁዶች ባሕርይ አደጋ ነው ብለው ይጠሩታል፡፡ አንድ የመንግስት ባለስልጣን ደግሞ ስደተኞቹን እንደ ካንሰር ናቸው ብሏል፡፡ ተክሊት ሚካኤል የ29 ዓመት እድሜ ያላት በቴል አቪቭ የምትኖር ከኤርትራ የመጣች ጥገኝነት ጠያቂ ስትሆን እስራኤል ይፋ ባደረገችው አዲስ እቅድ መሰረት አፍሪካውያን ስደተኞችን ለሌሎች መንግስታት ገንዘብ በመክፈል እንዲወስዱ ማድረግ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ነው ትላለች፡፡
አንድ ስደተኛ በበኩሉ፤ በሩዋንዳና በኡጋንዳ ምን እንደሚገጥመን አናውቅም በምትኩ በእስራኤል እስር ቤቶች መቆየትን እንመርጣለን ሲል ለሮይተር ገልጿል፡፡ ኔታንያሁ በቴል አቪቭ ከተማ አካባቢ ባሉ በጣም ድሀ በሆኑ አጎራባቾች አካባቢ ግዙፍ ቁጥር ያላቸው የአፍሪካ ስደተኞች እንደሚኖሩ በዚህም ምክንያት በአካባቢው ነባር የሆኑ እስራኤላውያን ነዋሪዎች ደሕንነት እንደማይሰማቸው ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ለደቡብ ቴል አቪቭ እንዲሁም በሌሎችም በርካታ አጎራባቾች ለሚኖሩ ነዋሪዎች ዛሬ መረጋጋትን ለመፍጠር የግለሰብ ደሕንነትን ለመጠበቅ ሕግና ስርዓትን ለማስከበር የገባነውን ቃል ጠብቀናል ሲሉ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ የእስራኤል የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አሪየህ ዴሪነ እንዲሁም የሕዝብ ደሕንነት ሚኒስትር ጊላድ ኤርዳን ይፋ ያደረጉት ዕቅድ አሳሳቢ መሆኑን ገልጿል፡፡ በእነዚህ አዲስ የእስራኤል መንግስት ዕቅዶች መሰረት የኤርትራና የሱዳን ጥገኝነት ጠያቂዎችና ስደተኞች አፍሪካ በሚገኙ ሌሎች ሀገራት እንዲዛወሩ ይህንንም ወደው እንዲቀበሉ ይገደዳሉ፡፡ ካልተቀበሉ እስራኤል ውስጥ እስር ቤት ይገባሉ፡፡
እ.አ.አ መጋቢት 2015 የእስራኤል መንግስት አወዛጋቢ በሆነውና በኃይል ወደሌላ ቦታ የማዛወር ፖሊሲን ተግባራዊ ለማድረግ ያስተ ዋወቀውን ፖሊሲ በተመለከተ ሕገወጥ ስደተኞች እስራኤልን ለቀው በሦስተኛ ሀገራት የተወሰነ መጠለያ እንዲያገኙ ዕድል የሰጠ ነው፡፡
እ.አ.አ ከታህሳስ 2013 እስከ ሰኔ 2017 ከዚህ ፕሮግራም መጀመሪያ አንስቶ አራት ሺ የሚሆኑ ኤርትራውያንና ሱዳናውያን በመንግስት መርሐ ግብር መሰረት ወደ ሁለት የአፍሪካ ሀገራት ሩዋንዳና ኡጋንዳ በፈቃደኝነታቸው እንዲሄዱ ተደርጓል፡፡
ሕገወጥ ስደተኞችን በተመለከተ እስራኤል ያወጣችው ይህ አዲስ ፖሊሲ በከበበው ምስጢራዊነት፤ ተግባራዊነቱን በተመለከተ ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ሁኔታውን ለመከታተል በእነዚህ የአፍሪካ ሀገራት እንዲዛወሩ የተደረጉት ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ ከባድ እንደሆነበት ከወራት በፊት ባወጣው መግለጫ አመልክቶ ነበር፡፡
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እነዚህ ሰዎች በቂ ደሕንነት ወይም በሄዱበት ዘላቂ መፍትሄ እንዳላገኙና በርካታዎቹ አደገኛ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ወደ አፍሪካ ወይም ወደ አውሮፓ ለመንቀሳቀስ ጥረት ማድረጋቸው ስለማይቀር ሁኔታው ያሳሰበው መሆኑን ገልጿል፡፡
እንደ 1951 የስደተኞች ኮንቬንሽን መሰረት እስራኤል ስደተኞችንም ሆነ ዓለምአቀፍ ጥበቃ የሚፈልጉ ሌሎች ሰዎችን የመጠበቅና የመከላከል ግዴታ አለባት ሲሉ የድርጅቱ የመከላከል ረዳት ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ ተናግረዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽንና ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ እስራኤል ዓለም አቀፍ ግዴታዋን እንድትወጣ ሲረዷት ቆይተዋል፡፡ይህም መልሶ በማስፈር ወይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከእስራኤል እንዲወጡ ለተደረጉት ሁለት ሺ400 ስደተኞች ዘላቂ የሆነ መፍትሄ እንድትፈልግ ማድረግን ያካትታል፡፡
በአሁኑ ሰዓት 27 ሺ 500 ኤርትራውያንና ሰባት ሺ800 የሚሆኑ ሱዳናውያን በእስራኤል ይገኛሉ፡፡ እ.አ.አ በ2009 እስራኤል የስደተኞችን ደረጃ እንድትወስን ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ከተሰጣት በኋላ ስምንት ኤርትራውያንና ሁለት ሱዳናውያን ብቻ ናቸው በሕጋዊ ደረጃ በባለስልጣናት የሚታወቁት፡፡

Published in ዓለም አቀፍ

እስራኤል በሕገወጥ መንገድ በሀገሯ የሚኖሩ ብዙ ሺ አፍሪካውያን ስደተኞች ገንዘብ እየሰጠች ለማስወጣት ውሳኔ አሳልፋለች፡፡ ስደተኞቹ በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ካልወጡ ግን ከመጋቢት መጨረሻ በኋላ እንደምታስርም ሮይተርስ ዘግቦታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ በግልጽ በካቢኔ ስብሰባ ላይ የአፍሪካ ስደተኞችን የክፍያ ፕሮግራም አስመልክተው ሲናገሩ ስደተኞች ወደመጡበት ሀገር ወይም ወደ ሦስተኛ ሀገር እንዲሄዱ ይደረጋል ሲሉ በይፋ ለሕዝብ ተናግረዋል፡፡
እስራኤል በ2013 ከግብጽ ጋር በሚያገናኛት ድንበር ሕገወጥ ስደተኞች ወደግዛቷ ማለፍ እንዳይችሉ ማገጃ ገንብታ ጨርሳለች፡፡ ይህ የማገጃ መስመር በመሰራቱ እስራኤል ሙሉ በሙሉ ውጤታማ በሆነ መልኩ ወደሀገሯ በሕገወጥ መንገድ የሚገቡትን ስደተኞች ማስቆምና መግታት ችላለች፡፡ ማገጃው ከመሰራቱና ከመጠናቀቁ በፊት ሰልሳ ሺ ያህል ከአፍሪካ የፈለሱ ሕገወጥ ስደተኞች በግብጽ በኩል ያለውን በረሀ አቋርጠው ወደ እስራኤል ገብተዋል፡፡
ወደ እስራኤል የገቡት ብዛት ያላቸው ሕገወጥ ስደተኞች የመጡት ከኤርትራና ሱዳን ሲሆን ብዙዎች እንደሚሉት የተሰደዱት በአገራቸው ያለውን ጦርነትና ግድያ በመሸሽ እንዲሁም ከባድ በሆነ የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ነው፡፡ ሆኖም እስራኤል በኢኮኖሚ ስደተኝነት ነው ያስተናገደቻቸው፡፡ እስራኤል ይፋ ባደረገችው እቅድ መሰረት ለአፍሪካ ስደተኞች ሦስት ሺ500 ዶላር (2900 ፓውንድ) ክፍያ በመስጠት ወደሀገራቸው እንዲመለሱ ወይም ወደሦስተኛ ሀገር እንዲሄዱ እንዲሁም ነጻ የአየር መጓጓዣ ትኬት ከእስራኤል መንግስት ይሰጣቸዋል፡፡የሰብዓዊ መብት ቡድኖች ሦስተኛ ሀገር የተባሉት ሩዋንዳና ኡጋንዳ መሆናቸውን ለይተዋል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ቀደም ባሉት ግዜያት ወደ 20ሺ ሕገወጥ ስደተኞችን አስወጥተናል፤ አሁን ያለው ግዳጅ ቀሪዎቹን መሸኘት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የስደተኞች መስሪያ ቤት ባለስልጣን፤ እስራኤል ውስጥ በሕገወጥ የሚኖሩ 38 ሺ የሚደርሱ ስደተኞች እንዳሉ አስታውቀዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንድ ሺ420 የሚሆኑት በሁለት የእስር ማእከሎች እንደሚገኙ ከመጋቢት በፊት በፈቃዳቸው ሀገሪቱን ለሚለቁት አነስተኛ ክፍያ የሚሰጥ መሆኑን የገንዘቡ መጠን ጊዜው ሲጨምር እያነሰ እንደሚሄድ ሕገወጥ ስደተኞቹ በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ተጠቅመው እስራኤልን ለቀው የማይወጡ ከሆነ አስገዳጅ የማሰር እርምጃዎች የሚጀመሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አንዳንዶቹ ለጥቂት ዓመታት በእስራኤል በመኖር በጣም ዝቅተኛ ክፍያ ባላቸውና ብዙ እስራኤላውያን በማይፈልጓቸው ስራዎች ተሰማርተው ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡እስራኤል ከአጠቃላዩ አንድ በመቶ ለሚያንሱት ስደተኞች ጥገኝነት እንዲሰጣቸው ላመለከቱትና ከዓመት በላይ የቆየ ማመልከቻ ላላቸው ጥቂቶች ብቻ ጥገኝነት ሰጥታለች፡፡ እስራኤል የአፍሪካ ስደተኞችን የጥገኝነት ጥያቄ ሂደት ታዘገያለች ይህም በፖሊሲዋ ምክንያትና ጥያቄውን ሕጋዊ አድርጋ ባለመቀበል ነው ሲሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ይከሷታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ የስደተኞች በእስራኤል መገኘት ለእስራኤል ማሕበራዊ ትስስርና ለአይሁዶች ባሕርይ አደጋ ነው ብለው ይጠሩታል፡፡ አንድ የመንግስት ባለስልጣን ደግሞ ስደተኞቹን እንደ ካንሰር ናቸው ብሏል፡፡ ተክሊት ሚካኤል የ29 ዓመት እድሜ ያላት በቴል አቪቭ የምትኖር ከኤርትራ የመጣች ጥገኝነት ጠያቂ ስትሆን እስራኤል ይፋ ባደረገችው አዲስ እቅድ መሰረት አፍሪካውያን ስደተኞችን ለሌሎች መንግስታት ገንዘብ በመክፈል እንዲወስዱ ማድረግ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ነው ትላለች፡፡
አንድ ስደተኛ በበኩሉ፤ በሩዋንዳና በኡጋንዳ ምን እንደሚገጥመን አናውቅም በምትኩ በእስራኤል እስር ቤቶች መቆየትን እንመርጣለን ሲል ለሮይተር ገልጿል፡፡ ኔታንያሁ በቴል አቪቭ ከተማ አካባቢ ባሉ በጣም ድሀ በሆኑ አጎራባቾች አካባቢ ግዙፍ ቁጥር ያላቸው የአፍሪካ ስደተኞች እንደሚኖሩ በዚህም ምክንያት በአካባቢው ነባር የሆኑ እስራኤላውያን ነዋሪዎች ደሕንነት እንደማይሰማቸው ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ለደቡብ ቴል አቪቭ እንዲሁም በሌሎችም በርካታ አጎራባቾች ለሚኖሩ ነዋሪዎች ዛሬ መረጋጋትን ለመፍጠር የግለሰብ ደሕንነትን ለመጠበቅ ሕግና ስርዓትን ለማስከበር የገባነውን ቃል ጠብቀናል ሲሉ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ የእስራኤል የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አሪየህ ዴሪነ እንዲሁም የሕዝብ ደሕንነት ሚኒስትር ጊላድ ኤርዳን ይፋ ያደረጉት ዕቅድ አሳሳቢ መሆኑን ገልጿል፡፡ በእነዚህ አዲስ የእስራኤል መንግስት ዕቅዶች መሰረት የኤርትራና የሱዳን ጥገኝነት ጠያቂዎችና ስደተኞች አፍሪካ በሚገኙ ሌሎች ሀገራት እንዲዛወሩ ይህንንም ወደው እንዲቀበሉ ይገደዳሉ፡፡ ካልተቀበሉ እስራኤል ውስጥ እስር ቤት ይገባሉ፡፡
እ.አ.አ መጋቢት 2015 የእስራኤል መንግስት አወዛጋቢ በሆነውና በኃይል ወደሌላ ቦታ የማዛወር ፖሊሲን ተግባራዊ ለማድረግ ያስተ ዋወቀውን ፖሊሲ በተመለከተ ሕገወጥ ስደተኞች እስራኤልን ለቀው በሦስተኛ ሀገራት የተወሰነ መጠለያ እንዲያገኙ ዕድል የሰጠ ነው፡፡
እ.አ.አ ከታህሳስ 2013 እስከ ሰኔ 2017 ከዚህ ፕሮግራም መጀመሪያ አንስቶ አራት ሺ የሚሆኑ ኤርትራውያንና ሱዳናውያን በመንግስት መርሐ ግብር መሰረት ወደ ሁለት የአፍሪካ ሀገራት ሩዋንዳና ኡጋንዳ በፈቃደኝነታቸው እንዲሄዱ ተደርጓል፡፡
ሕገወጥ ስደተኞችን በተመለከተ እስራኤል ያወጣችው ይህ አዲስ ፖሊሲ በከበበው ምስጢራዊነት፤ ተግባራዊነቱን በተመለከተ ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ሁኔታውን ለመከታተል በእነዚህ የአፍሪካ ሀገራት እንዲዛወሩ የተደረጉት ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ ከባድ እንደሆነበት ከወራት በፊት ባወጣው መግለጫ አመልክቶ ነበር፡፡
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እነዚህ ሰዎች በቂ ደሕንነት ወይም በሄዱበት ዘላቂ መፍትሄ እንዳላገኙና በርካታዎቹ አደገኛ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ወደ አፍሪካ ወይም ወደ አውሮፓ ለመንቀሳቀስ ጥረት ማድረጋቸው ስለማይቀር ሁኔታው ያሳሰበው መሆኑን ገልጿል፡፡
እንደ 1951 የስደተኞች ኮንቬንሽን መሰረት እስራኤል ስደተኞችንም ሆነ ዓለምአቀፍ ጥበቃ የሚፈልጉ ሌሎች ሰዎችን የመጠበቅና የመከላከል ግዴታ አለባት ሲሉ የድርጅቱ የመከላከል ረዳት ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ ተናግረዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽንና ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ እስራኤል ዓለም አቀፍ ግዴታዋን እንድትወጣ ሲረዷት ቆይተዋል፡፡ይህም መልሶ በማስፈር ወይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከእስራኤል እንዲወጡ ለተደረጉት ሁለት ሺ400 ስደተኞች ዘላቂ የሆነ መፍትሄ እንድትፈልግ ማድረግን ያካትታል፡፡
በአሁኑ ሰዓት 27 ሺ 500 ኤርትራውያንና ሰባት ሺ800 የሚሆኑ ሱዳናውያን በእስራኤል ይገኛሉ፡፡ እ.አ.አ በ2009 እስራኤል የስደተኞችን ደረጃ እንድትወስን ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ከተሰጣት በኋላ ስምንት ኤርትራውያንና ሁለት ሱዳናውያን ብቻ ናቸው በሕጋዊ ደረጃ በባለስልጣናት የሚታወቁት፡፡

Published in ዓለም አቀፍ
Thursday, 11 January 2018 19:54

የፌዴራል ስርዓቱ ባለቤት

ኢትዮጵያ ቡራቡሬ ሃገር ናት፤ የሰማንያ የተለያዩ ብሄራዊ ማንነቶች የፈጠሩት ቡራቡሬ፤ አንድ አካል ላይ ያሉ የተለያዩ ማንነት ያላቸው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የፈጠሩት ውብ ህብረ ብሄራዊነት። በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነት የምንለው ይህን አንድ ሃገር የመሰረተ ህብረብሄራዊነት ነው። ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ገጽታዋ በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነት ወይም ህብረብሄራዊነት/ ብዝሃነት ነው። ይህ ተጨባጭ እውነት ነው።
ኢትዮጵያ የተለያየ ማንነት ያላቸው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሃገር ብትሆንም ብዝሃነት እውቅና የተሰጠው ግን ከ1983 በኋላ ነው። ከዚያ ቀደም የነበሩት ስርዓቶች ልዩነቱን በሃይል አጥፍተው አንድ ብሄራዊ ማንነት ያላት ሃገር ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ናቸው። ይህ ብዝሃነትን ወይም በልዩነት ውስጥ ያለን አንድነት በማጥፋት አንድ ማንነት ያላት ሃገር የመመስረት ስትራቴጂ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ጀምሮ ለአንድ ክፍለ ዘመን ያህል ሥራ ላይ ውሏል።
የብሄር ብዝሃነትን በማጥፋት አንድ ማንነት ያላት ሃገር የመመስረት ስትራቴጂው በኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። የትኛውም ብሄር ወይም ብሄረሰብ ማንነቱን ለሌላ የእርሱ ላልሆነ ማንነት መስዋዕት በማድረግ የማንነቱ መገለጫዎች እንዲጠፉ የመፍቀድ ፍላጎት አልነበረውም።
እንግዲህ አሁን ከጎልማሳነት እድሜ በላይ የሆንን ኢትዮጵያውያን ሁሉ እንደምናስታውሰው ቀደም ባሉትና የሃገሪቱን ብዝሃነት ያልተቀበሉ ስርዓቶች በነበሩበት ዘመን ከራሳቸው ቋንቋ ውጭ መግባባት የማይችሉ በግርድፍ ግምት ከ85 በመቶ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የመንግሥት አገልግሎት የሚያገኙት በማያውቁት ቋንቋ ነበር። ፍርድ ቤት ቆመው ጉዳያቸው ላይ ምንም በማያውቁት ቋንቋ እንዲሟገቱ ይገደዱ ነበር። በማያውቁት ቋንቋ መሟገት ምን ያህል እንደሚከብድና እንደሚያሸማቅቅ አስተውሉ። አፍ ከከፈቱበት ቋንቋ ውጭ ምንም ሰምተው የማያውቁ ህጻናት ፈጽሞ ባዕድ በሆነ ቋንቋ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ለመማር ይገደዱ ነበር።
የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የኑሮ ዘይቤ መገለጫ የሆኑ ባህሎች ይራከሱ ነበር። ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህላቸውን የማሳደግ ዕድል አልነበራቸውም። በባህላቸው እንዲያፍሩና እንዲሸማቀቁ ይደረግ ነበር። ታሪካቸው በተዛባ መልክ ይቀርብ ነበር። እውነተኛ ታሪካቸውን የማጥናት፣ የመጻፍ፣ የመንከባከብ መብት አልነበራቸውም። በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በማንነታቸው እንዲሸማቀቁ ይደረግ ነበር። ይህ ሆን ተብሎ ነበር የሚደረገው። የተለያዩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች ተወላጆች በቋንቋቸው የወጣላቸውን መጠሪያ ስም ይቀይሩ የነበረው ማንነታቸውን ይፋ ወጥቶ ለአሸማቃቂ ተረብ እንዳይጋለጡ በመስጋት መሆኑን ልብ በሉ። እርግጥ ቀደም ባሉት ጊዜያት የመንግስት የሥራ እድልም ለማግኘት ማንነትን መሸሸግ ያስፈልግ ነበር።
የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከብሄራዊ ጭቆና በተጨማሪ ለኢኮኖሚ ጭቆናም ተዳርገው ነበር። በዘውዳዊው ስርዓት፣ ኑሯቸው በግብርና ላይ የተመሰረተ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች አርሶ አደሮች መሬት አልባ ነበሩ። ዘርማንዘራቸው አቅንቶ ሲጠቀምበት የኖረውን መሬታቸውን ተነጥቀው መሬቱ ለመሳፍንቱ፣ መኳንንቱ፣ በተለያየ ደረጃ ለሚያገለግሉ የመንግስት ተሿሚዎች እንዲሁም ለንጉሰ ነገስቱና መሳፍንቱ ወዳጆች ተሰጥቶ ቆይቷል። ታዲያ፣ መሬታቸውን የተነጠቁት ባለሃገር አርሶ አደሮች በገዛ መሬታቸው ላይ ለገባር ጭሰኝነት ተዳርገዋል። የራሳቸውን መሬት አርሰው ምርቱን መሬታቸውን ለነጠቃቸው ባለርስትና ባለጉልት ይገብራሉ፤ ጉልበታቸው ላይ የማዘዝ መብትም አልነበራቸውም።
እንግዲህ ይህ ከላይ በአጭሩ የተገለጸው በኢትዮጵያ የነበረ ታሪካዊ ነባራዊ ሁኔታ ነው። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይህን አስከፊና ክብረ ነክ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አሜን ብለው አልተቀበሉም። አቅምና ሁኔታዎች በፈቀዱት ልክ ለመታገል ሞክረዋል። የመጀመሪያዎቹ የትግል እንቅስቃሴዎች በአጥቢያ የተወሰኑ፣ ያልተደራጁና ድንገት የሚገነፍሉ አመጾች ነበሩ። በየአካባቢው የስርዓቱ ሹመኞች ላይ ከተካሄዱና የአውራጃ ከተማ እንኳን ሳይሰሙ ከከሰሙ አመጾችና ተቃውሞዎች ባሻገር፣ በሃገር አቀፍ ደረጃ ለመሰማት የበቁ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችም ነበሩ። የትግራይ ቀዳማይ ወያኔ እና የባሌ አርሶ አደሮች አመጽ ከእነዚህ መሃከል ተጠቃሾች ናቸው።
በአጠቃላይ ቀደምቶቹ ብሄራዊና ኢኮኖሚያዊ ጭቆና የወለዳቸው ተቃውሞዎችና አመጾች በወጉ ያልተደራጁና መርህ ላይ የተመሰረቱ አልነበሩም። ከዚህ ይልቅ በአጋጣሚ የሚፈነዱና አካባቢያዊ ነበሩ። በመሆኑም አርሶ አደሩን ለእስር፣ ለመቀጣጫነት ገበያ መሃል በጅራፍ ለመገረፍ ከመዳረግ አልፈው ለውጥ ማምጣት አላስቻሉም። መርህ ላይ የተመሰረቱ ሳይሆኑ ግብታዊ ስለነበሩ ቦግ ብለው እልም የሚሉ የአፍታ ተቃውሞዎች ከመሆን ሳይዘሉ ቆይተዋል።
እየከራረመ አነሰም በዛም ከየብሄሩ የመማር ዕድል ያገኙ ልሂቃን ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ። እነዚህ ልሂቃን የብሄራዊና የኢኮኖሚ ጭቆናውን ስረ መሰረት በመተንተን ምንጩን በማጋለጥ በመርህ ላይ የተመሰረተ የነጻነትና የእኩልነት ትግል ማካሄድ የሚቻልበትን ሁኔታ አመላከቱ። በኋላም በዚህ ላይ ተመስርተው የብሄራዊ ነጻነት እንቅስቃሴዎች ተጀመሩ። በወቅቱ የዜጎች የፈቀዱትን አመለካከት የመያዝ፣ አመለካከትን የመግለጽ፣ የመደራጀት፣ በግልም ይሁን ከመሰሎች ጋር በመደራጀት አመለካከትን የማራመድ ወዘተ ነጻነት በህግ የተገደበ ስለነበረ፣ የብሄራዊ ነጻነትና እኩልነት ጥያቄ አንግበው የተነሱት እንቅስቃሴዎች የነበራቸው አማራጭ ብረት አንስተው የትጥቅ ትግል ማካሄድ ብቻ ነበር። እናም በተለይ ከ1960ዎቹ አጋማሽ በኋላ እስከ ሃያ የሚደርሱ የብሄራዊ ነጻነት ቡድኖች ተደራጅተው የትጥቅ ትግል ማካሄድ ጀምረዋል። በኢትዮጵያ የብሄራዊ ነጻነት የትጥቅ ትግል እንዲጀመር ያደረገው ታሪካዊ ነባራዊ ሁኔታ ከላይ የተገለጸውን ይመስላል።
እነዚህ የትጥቅ ትግል በማካሄድ ላይ የነበሩ የብሄራዊ ነጻነት ቡድኖች ህዝቡ ውስጥ ሰርጸው በገቡበት መጠን፣ በተዋጊ ሃይል ብዛት፣ በወታደራዊ አቅም፣ በመርህና መስመር ጥራት የሚበላለጡ ቢሆንም ሁሉም ለብሄራዊ ነጻነት የሚታገሉ ነበሩ። ይህ ተመሳሳይነት የአንድ ታሪካዊ ነባራዊ ሁኔታ ውጤት መሆናቸውን ያመለክታል። ዓላማቸውን በህዝብ ውስጥ ያሰረጹበት ደረጃ፣ የመርህና የመስመር ጥራታቸው፣ የተዋጊ ሃይልና ወታደራዊ አቋም ጥንካሬ ላይ የነበራቸው ልዩነት ደግሞ አሃዳዊውን ስርዓት በመጣል ረገድ ያላቸው ተሳትፎ እንዲለያይ አድርጓል። ይህ ተጨባጭ እውነታ ነው።
ያም ሆነ ይህ የመጨረሻው አሃዳዊ የወታደራዊ ደርግ የመንግሥት ስርዓት እነዚህ የብሄራዊ ነጻነት ግንባሮች በየአካባቢው ባካሄዱት ትግል ነበር የፈራረሰው። ቀደም ሲል እንደገለጽኩት የብሄራዊ ነጻነት ንቅናቄዎቹ በውጊያ አቅም የነበራቸው ድርሻ ቢለያይም ስርዓቱን በማስወገዱ ሂደት ውስጥ ግን ሁሉም ድርሻ ነበራቸው ማለት ይቻላል። ወታደራዊው ደርግ ለመወገድ የበቃው በአጋጣሚ ሳይሆን የሃገሪቱ ታሪካዊ አስገዳጅ ሁኔታ በፈጠረው የብሄራዊ ነጻነት ትግል ነው።
በደርግ ውድቀት ማግስት ኢትዮጵያ የመበታተን አፋፍ ላይ ቆማ ነበር። በየአካባቢው ይንቀሳቀሱ የነበሩ የብሄራዊ ነጻነት ግንባሮች የሚወክሏቸው ብሄሮችና ብሄረሰቦች የሚኖሩባቸውን አካባቢዎች ወደ መቆጣጣር ሄደው ነበር። ይሁን እንጂ ተበታትነው ትንንሽ ነጻ ሃገር ከመመስረት ይልቅ፣ ጨቋኝ ስርዓት ስር በነበሩበትም ጊዜ ቢሆን ባካበቷቸው መልካም የጋራ እሴቶች ላይ በመመስረት ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ መብትና ነጻነቶቻቸው ተከብረው፣ በእኩልነትና በመከባበር ላይ በተመሰረተ አንድነት አብረው መኖር የሚችሉበት ዕድል ይኖር እንደሆነ ያለማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት ለመምከር ሸንጎ ተቀመጡ፤ ደርግ በተወገደ በወሩ ሰኔ 1983 ዓ/ም ላይ።
የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በእኩልነት መኖር የሚችሉበት ፌዴራላዊ ስርዓት መሰረት የተጣለው በዚህ ሸንጎ ነበር። በሸንጎው ላይ ሁሉም ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በእኩልነት የሚኖሩበት የህዝቦች አንድነት ያለው ሃገር መመስረት የሚያስችላቸውን ህገመንግስት ለመቅረጽ ተስማሙ። ይህን ህገመንግስት የሚቀርጹበት የሽግግር መንግስትም መሰረቱ። በዚህ የሽግግር ወቅትም ቢሆን በአሃዳዊው ስርዓት መዋቅር ለመኖር አልፈቀዱም። የሽግግር መንግስቱ እንደ ህገመንግስት በሚጠቀምበት ቻርተር ላይ ራሳቸውን ለማስተዳደር በሚያስችላቸው ሁኔታ ነበር የተዋቀሩት። በዚህ የሽግግር መንግስት ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦች በተሳተፉበትና ስምምነታቸውን በገለጹበት ሁኔታ የኢፌዴሪ ህገመንግስት ተቀረጸ። ይህ ህገመንግስት አሁን ያለው ፌዴራላዊ ስርዓት የተመሰረተበት ህገመንግስት ነው።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ፣ በእኩልነትና በመከባበር ላይ በተመሰረተ አንድነት የሚኖሩበት ፌዴራላዊ ስርዓት የተመሰረተው በአንድ ቡድን ፍላጎት ሳይሆን በኢትዮጵያ በነበረው ታሪካዊ ነባራዊ ሁኔታ ገፊነት ነው። ይህ ታሪካዊ ሁኔታ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብትና ነጻነታቸውን እንዲሹ ያደረገ በመሆኑ ፌዴራላዊ ስርዓቱ በኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት የመጣ ነው። የስርዓቱ ባለቤቶችም ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው። ይህን ፌዴራላዊ ስርዓት መጋፋት የኢትዮጵያን ህዝብ መጋፋት ነው፤ ምናልባት ሃገሪቱን ወደ መፍረስ ከመግፋት ያለፈም የሚያስገኘው ፋይዳ የለም።

Published in አጀንዳ

የአገራችን ግብርና ውጤቶች በምርታማነትም ሆነ በጥራት ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በስፋት ጥቅም ላይ አለመዋሉ እክል ሆኖ መኖሩ በምክንያትነት ይነሳል፡፡ በተለይ አብዛኛው አርሶ አደር በአነስተኛ ማሳ የሚጠቀም በመሆኑ እንደ ትራክተር ያሉ ዘመናዊ መሳሪያዎችን የመጠቀም ልምዱ አነስተኛ እንዲሆን እንዳደረገው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ለአብነት በትራክተር ብዛት ከምሥራቅ አፍሪካ አገራት ጋር ያለውን ንጽጽር ማየት ይቻላል፡፡ ለ10 ሺ ሄክታር በኢትዮጵያ 2 ነጥብ 24 ትራክተር ያለ ሲሆን፤ ሱዳን 9 ነጥብ 61፣ ኤርትራ 7 ነጥብ 12፣ ሶማሊያ 12 ነጥብ 06 ፣ ኬንያ 26 ነጥብ 28 ትራክተር አላቸው፡፡
በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ከ80 በመቶ በላይ የምርት እድገት አነስተኛ አርሶ አደሮች በሚያስመዘግቡት የምርት መጨመር እንደሚመጣ እንዲሁም በእቅድ ዘመኑ የዋና ዋና ሰብሎችን የድኅረ ምርት ብክነት አሁን ካለበት ከ15 እስከ 25 በመቶ ወደ 5 በመቶ ዝቅ ለማድረግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ማላመድና መጠቀም ወሳኝ ነው፡፡ ከእዚህ ባሻገር የምግብ ዋስትናን በቤተሰብ ደረጃ ከማረጋገጥ አልፎ ወደ ኢንደስትሪ ለመሸጋገር የተያዘውን እቅድ ለማሳካት፤ ግብዓት የሚያቀርብ ግብርና ለማጠናከርና እሴት ተጨምሮ የውጭ ምንዛሪ የሚስያገኝ ዘርፍ ለመፍጠር ሜካናይዜሽን አስፈላጊነቱ ከፍተኛ ነው፡፡
የግብርና ሜካናይዜሽንን ወሳኝ ሚና የተገነዘበው መንግሥት በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመን መጀመሪያ 3 በመቶ የነበረውን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ አርሶ አደር 53 በመቶ ለማድረስ ግብ አስቀምጧል፡፡ በአሁኑ ወቅትም 11 በመቶ ማድረስ ተችሏል፡፡ በአርሶ አደሩ ዘንድ ግንዛቤውን ለማስፋትም በተያዘው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የግብርና ሜካናይዜሽን ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲከበር ተደርጓል፡፡ ይሁንና የተያዘውን ግብ ለማሳካትና ከትሩፋቱም ለመቋደስ የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠልና ያሉትን ጉድለቶች እየፈተሹ ማሟላት እንደሚገባ በገሃድ የሚታየው ነባራዊ ሃቅ ይጠቁማል፡፡
የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት በአነሰተኛ ማሳ የሚካሄደው የግብርና ልማት የፈጠረውን እክል ለመቀነስ የክላስተር እርሻን የማጠናከሩ ጉዳይ ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ባለፉት ዓመታት አመርቂ ወጤት የተገኘ ሲሆን አሁንም ግንዛቤውን በማስፋት የተጠቃሚ አርሶ አደሮችን ቁጥር የማበራከቱ ጉዳይ ሊጠናከር ይገባል፡፡ ለእዚህም በየቀበሌው የተመደቡ የግብርና ባለሙያዎች ሚናቸውን መወጣት አለባቸው፡፡
የአገሪቱ ዋንኛ የኢኮኖሚ ምንጭ ግብርና የመሆኑን ያህል ቴክኖሎጂን በመቅዳትና በማላመድ እንዲሁም አርሶ አደሩ ድረስ በመውረድ አጠቃቀሙን፣ ሲበላሽም እንዴት እንደሚጠገን የሚያሰለጥን ባለሙያ በማፍራት ረገድ ከፍተኛ ውስንነት ይታያል፡፡ ለእዚህ አሁን ቁጥራቸው እየተበራከተ የመጣው ዩኒቨርሲቲዎች እና የቴክኒክ ኮሌጆች የመፍትሄ አቅጣጫ የመተለም ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ እንደ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ምርምር ማድረግ፣ ስርዓተ ትምህርት መቅረጽና ባለሙያ ማፍራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
የግብርና ምርምር ማዕከላት የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገቡ ቴክኖሎጂዎችን የማውጣት ተግባራቸው እንዲጠናከር ተገቢው እገዛ ሊደረግላቸው ይገባል፤ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሮቹ የማስተዋወቅና እንዲጠቀሙበት የማስተማር ሃላፊነት የተጣለባቸውም ተቋማትም ሚናቸውን ይወጡ፡፡
የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን የሚያመርቱ፣ ከውጭ አገር የሚያስገቡና በኪራይ አገልግሎት የሚሰጡ የግል ባለሀብቶችን የሚያበረታታ ስርዓት መዘርጋትም እንደ መፍትሄ መወሰድ አለበት፡፡ ዘርፉ ዓለም ከደረሰበት ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ ወደ ኋላ የቀረበት ዘመን እንዲካካስ የቀረጥ ነጻና ሌሎች የማበረታቻ ፓኬጆች ተቀርጸው ቢተገበሩ የሚጠበቀው ውጤት ይመዘገባል፡፡ የግል ባለሃብቶች ሚና እንዲጠናከር የብድር አገልግሎት የሚመቻችበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ ለእዚህም ባለድርሻ አካላት በጋራ በመምከር ተጨባጭ እቅድ ማቅረብና ወደ ተግባር በመግባቱ ሂደትም ተገቢውን ሚናቸውን መወጣት አለባቸው፡፡
ዛሬ የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎች በምርታማነት፣ በጥራት እንዲሁም ብክነትን ከማዳንና ከሌሎችም ትሩፋታቸው ባሻገር አርሶ አደሩ በስፋት ልጆቹን ዘመናዊ ትምህርት እንዲቀስሙ ከሚያደርገው ጥረት አንጻር የሚፈጠረውን የሰው ሀይል እጥረትም ከመፍታት አኳያ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ታምኖበታል፡፡ የግብርና ሜካናይዜሽን በከፍተኛ ደረጃ የሰው ሀይል ከሚጠቀመው የግብርና ዘርፍ ጋር ተያይዞ ብዙዎችን ሥራ ያሳጣል የሚለው ስጋት ሚዛን የማይደፋና ይልቁንም የአርሶ አደሩን ልጅ ጨምሮ በሂደት ለበርካቶች ሥራ የሚፈጥር ዘርፍ መሆኑ ስለታመነበት ዘመኑ የሚጠይቀውን ስር ነቀል ለውጥ ማካሄድ ይገባል፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

የጥቃቅንና አነስተኛ ጉዳይ በተነሳ ቁጥር ከተደራጁ ወጣቶች ተደጋግሞ የሚነሳው ቅሬታ የመስሪያ ቦታ ጉዳይ ነው፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅቶ መሥራት ውጤታማ እንደሚያደርግ የተለያዩ ወጣቶች በተለያየ ጊዜ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ የመስሪያ ቦታ ችግር ግን ፈታኝ እንደሆነባቸውም ቅሬታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ ጉዳዩ የሚመ ለከታቸው አካላት ደግሞ አዳዲስ እየተሠሩ እንደሆነ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ 422 ሼዶችን አስገንብቶ ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል፡፡ ሼዶቹም ለተለያዩ አይነት ሥራዎች የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ሼዶች በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ሳንባ ነቀርሳ ሆስፒታል አካባቢ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ጀሞ መድሃኒለም፣ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ እና ዘጠኝ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል አካባቢ፣ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ቂሊንጦ፣ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ሰሚት ኮንዶሚኒየም አካባቢዎች የተገነቡ ናቸው፡፡
በጉለሌ ክፍለ ከተማ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጉዕሽ ተክለመድህን እንደሚሉት፤ በሳንባ ነቀርሳ ሆስፒታል አጠገብ ያለው የመስሪያ ቦታ በዋናነት የሚያገለግለው ለደረቅ ምግቦች ዝግጅት ነው፡፡ ይህም እንዲሆን የተደረገው በወጣቶች ፍላጎትና ያለውን ተፈላጊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡
የመስሪያ ቦታው በውስጡ 25 ሼዶችን የያዘ ሲሆን፤200 ወጣቶችን በኢንተርፕራይዝ አደራጅ ቷል፡፡ እነዚህ ወጣቶች በኢንተርፕራይዝ የተደራጁ ሲሆኑ በውስጣቸው ግን ብዙ ወጣቶችን ቀጥረው የሚያሠሩ ናቸው፡፡ ለ600መቶ ወጣቶች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይታሰባል፡፡ የመስሪያ ቦታው አሁን ሥራ ስላልጀመረ እንጂ ሲጀምር ሌሎች ሥራዎችንም እንደሚሠራ ነው አቶ ጉዕሽ የተናገሩት፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግንባታው ተጠናቆ መብራት ብቻ ነው የቀረው፡፡ መብራት እንዲገባም ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት ደብዳቤ ተልኮ በመጠበቅ ላይ ነው ያለው፡፡
ጀሞ አካባቢ በተገነባው የመስሪያ ቦታ ደግሞ 28 ሼዶች ይገኛሉ፡፡ አንዱ ሼድ ብቻ 50 ሰዎች ይይዛል፡፡ በውስጡ የሚሠሩትም የባልትና ውጤት ምርቶች፣ የእንጨትና ብረታብረት ሥራዎች ናቸው፡፡ በዚህ ቦታ ላይም ሥራ እንዳይጀመር ፈተና የሆነው መብራት ነው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ልዑልሰገድ ይፍሩ እንደሚሉት፤ ቢሮው በተለይም በዘንድሮው ዓመት ወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ ነው፡፡ በዚህም ለ61 ሺ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ ትልቅ ትኩረት የተሰጠውም በኮንስትራክሽን ዘርፍና በኮብልስቶን ንጣፍ ነው፡፡ እስከአሁንም 18 ሺ ወጣቶች ሠልጥነዋል፡፡ በብረታብረትና እንጨት፣ አልባሳትና ጨርቃጨርቅ በመሳሰሉት የማኑፋክቸሪንግ ሥራዎችም ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል፡፡ አሁን ላይ ተገንብተው የተጠናቀቁት የመስሪያ ቦታዎችም እነዚህን ሥራዎች ታሳቢ ተደርጎ የተሠሩ ናቸው፡፡
በቀጣይም ተመሳሳይ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችል ጥናት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየተጠና ነው፡፡ ይህም ለ113 ሺ ወጣቶች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል፡፡ በተጨማሪም በንግድና በአገልግሎት ዘርፍ ሥራዎች የገበያ ትስስር እንዲፈጠር ይሠራል፡፡ በአሁኑ ወቅት ተገንብተው የተጠናቀቁት ሼዶች ብቻ ለ10 ሺ ያህል ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው፡፡
‹‹የመስሪያ ቦታ መገንባት ብቻውን የሥራ ዕድል መፍጠር አይደለም›› የሚሉት አቶ ልዑልሰገድ ከራሳቸው ከወጣቶችም ሆነ ከሥራ አመራሮች ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ነው የሚያሳስቡት፡፡ በተለይም በሥራ ፈጠራ ግንዛቤ ላይ አሁንም ክፍተት ይታያል፡፡ ይህ የግንዛቤና የአመለካከት ክፍተት ካልተሞላ፣ ሥራ አመራሩም በቁርጠኝነት ካልሠራ የመስሪያ ቦታ ብቻውን የሥራ ዕድል አይፈጥርም፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አቶ ድሪባ ኩማ አሁን ከተጠናቀቁት በተጨማሪ 760 የመስሪያ ቦታዎችም እየተገነቡ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡ ይሁንና ተገንብተው የተጠናቀቁትም መብራት የማስገባትና የመስሪያ ማሽኖችን መትከል ይቀራል፡፡ በተጨማሪም 300 በህገ ወጥ የተያዙ ሼዶችም እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ በአጠቃላይ ከ12 ሺ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ታስቧል፡፡
የሚገነቡ ሼዶች በኢንዱስትሪ ክላስተር እንደሚሆንም ይናገራሉ፡፡ «ትላልቅ ኢንዱስትሪ የሚሠራባቸው ይሆናሉ፡፡ በኢንዱስትሪ ክላስተር ሲሠሩ እርስበርስ የመተጋገዝ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ አንዱ ኢንዱስትሪ ለሌላው ኢንዱስትሪ ምርት ማቅረብ ይችላል።» መስሪያ ቦታዎቹ በክላስር መሆናቸው እንደ መብራትና ውሃ የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶችን ለመጠቀም አመቺ መሆኑን አስረድተው፤ ይህ ዓይነት አሠራር በሌላው ዓለምም የተለመደ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
የተገነቡት ሼዶች ለወጣቶች የሚሰጡት በዕጣ እንደሆነ ነው ከንቲባው የተናገሩት፡፡ ብዙ የተደራጁ ወጣቶች ስላሉ እንደተደራጁበት ቅደም ተከተል በሂደት በዕጣ ይሰጣቸዋል፡፡ ይህም አሠራሩን ከአድሎ የፀዳ ያደርገዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ ሲተላለፉም ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አሠራር የሚከተል ይሆናል፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ወጣቶች የሚያመርቷቸውን ምርቶች ማስተዋወቅ እንደሚያ
ስፍልግ ነው ከንቲባው ያሳሰቡት፡፡ ለዚህም መንግሥት ምቹ የገበያ ትስስር እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡

ዜና ሐተታ
ዋለልኝ አየለ

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።