Items filtered by date: Friday, 12 January 2018

ይህ በባለ ታሪኩ የሰማነው የእውነት የሆነ ታሪክ ነው፡፡ የአትሌቱ ሰፈር ነዋሪ የሆኑት ኮሎኔል ተክሉ የያዟትን ቮልስ መኪና ሲያሽከረክሩ ፈረንሳይ ኤምባሲ አካባቢ ቁልቁለቱ ላይ አትሌቱን ያዩትና ‹‹ ዋሚቾ ልሸኝህ?›› ይሉታል፡፡ ዋሚም ‹‹ እቸኩላለሁ›› ብሎ መለሰላቸው፡፡ ከመኪናዋ ቀድሞ የሚፈለገው ቦታ ላይ ሲደርስ፤ ዘግይታ የደረሰችዋን መኪና እያፌዘባት ‹‹ የአንተ ቆርቆሮ እንደማታዋጣህ አየህ!›› አለ፡፡ ኮሎኔሉ በንግግሩ ተደንቆ ማታ ላይ ግብዣ አደረገላቸው፡፡ ‹‹ዋሚ እቸኩላለሁ›› አለ ተብሎ እንደቀልድ እየተወራ ዘመናትን የተሻገረ እውነታ ሆኗል፡፡
እኛም «ዋሚ እቸኩላለሁ» አለ እየተባሉ ለዘመናት የሚወራላቸውን የክብር ዶክተር አትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ በህይወት እያሉ ሥራዎቻቸውን ለመዘከር ወድደን ከገና በዓል ማግስት ከቤታቸው ተገኘን፡፡ እኝህ ሰው ሩጫና ፉክክር በኢትዮጵያ በወጉ እንዲታወቅ ካደረጉ ጥቂት ፊታውራሪዎች መካከል ከዋነኞቹ ጎራ ስለመሰለፋቸው በርካቶች ያነሳሉ፡፡ መረጃዎችን ስናገላብጥ ይህን አገኘን፡፡
አበበ ቢቂላ የሮምን ማራቶን በባዶ እግሩ ፉት ብሎ ካጠናቀቀ በኋላ በድጋሜ 42 ኪሎ ሜትር እንደሚሮጥ ሯጭ ሰውነቱን ሲያፍታታ የተመለከቱ ጋዜጤኞች በመገረም «አይደክምህም እንዴ?» በማለት በአድናቆት ሲጠይቁት፤ የአበበ መልስ ይበልጥ አስደንግጧቸው ነበር፡፡ ጋዜጠኞቹ ጠጋ ብለው ሲጠይቁትም «እኔ የዓለም አንደኛ፣ የኢትዮጵያ ግን ሁለተኛ ሯጭ ነኝ» ሲል መለሰላቸው፡፡ «እንዴት? ኢትዮጵያ ካንተም የተሻለ ሯጭ አላትን?» ሲሉም በድጋሚ ጠየቁት፤
«አዎን እሱ ስለታመመ እኔ ወዲህ መጣሁ፤ ቢመጣ ኖሮ ጀግንነቱን ትመለከቱ ነበር!» ሲል አበበ መለሰላቸው፡፡ ጋዜጠኞችም ተገረሙ፡፡ ተገርመውም ወሬውን አራገቡት፡፡ ኢትዮጵያ በሁለተኛ ሯጯ ድል አደረገች ሲሉም አጧጧፉት፡፡ አበበ ቢቂላ በኩራትና በአድናቆት አክብሮቱን የገለጸለት ታላቅ አትሌትም የክብር ዶክተር አትሌት ሻምበል ባሻ ዋሚ ቢራቱ ነበር፡፡
አንጋፋው የብስክሌት ተወዳዳሪ ገረመው ደንቦባም ‹‹ በኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ውድድር ላይ ማንም ሰው ተከትሎት አይገባም ነበር፡፡ ቁመናው፣ ጥንካሬው፣ ብርታቱ፣ ሁሉ ነገሩ ለሩጫ የተፈጠረ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያውቀውንና እንዲህ በአድናቆት የሚመለከተውን ሩጫ በሚገባ ያስተዋወቀ ዋሚ ነው፡፡ በየቀኑ ከሱሉልታ አዲስ አበባ ጠዋትና ማታ ይሮጥ ነበር::›› ማለቱም በማይነጥፈው ታሪክ ተከትቧል፡፡
ከተለያዩ አካላት እውቅና እየጎረፈላቸው የሚገኙት ጀግናው አትሌት ዋሚ ቢራቱ በቅርቡ በአሮሚያ ክልል አዳማ ከወንጂ ማዞሪያ እስከ ፈጣን መንገድ መግቢያ ድረስ ያለው መንገድ በስማቸው ተሰይሞላቸዋል፡፡ በህይወት እያሉ ይህንን ታሪክ ማየታችው ምን ያክል እንዳስደሰታቸው ለማወቅ ከእርሳቸውና ከ10ኛ ልጃቸው ጃገማ ዋሚ ጋር ቆይታ አደረግን፡፡
በህይወት እያሉ ይህ መደረጉ ምን ፈጠረብዎት? የመጀመሪያ ጥያቄያችን ነበር፡፡ ‹‹የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በእኔ ስም መንገድ በመሰየሙ ደስታዬ ወደር የለውም፡፡ ተግባሩ ትክክለኛና የሚገባ ነው፡፡ ለዚህም ክልሉ ሊመሰገን ይገባል፡፡ በወቅቱ ማህበረሰቡ በድምቀት በተሞላበት ሁናቴ አቀባበል ስላደረገለኝ ትልቅ አክብሮትና ምስጋና አለኝ፡፡ የተደረገልኝ ነገር በሙሉ ከውስጤ እንዳይጠፋ ተደርጎ ተስሏል፡፡›› ፈገግታ በተሞላበት ፊትና ሲቃ በታጀበበት አንደበት የመለሱልን ነው፡፡
አትሌቱ እንደሚሉት፤ ከዚህ ቀደም የተደረገ ላቸው የእውቅና የማዕረግ ሽልማት እያስገረማቸው በህይወት እያሉ ባልጠበኩበት ወቅት ይህን ማየታቸው ዕድለኛ አድርጓቸዋል፡፡ ለእርሳቸው የተደረገው መልካም ተግባር የኢትዮጵያና የአፍሪካ ህዝብ ብሎም የዓለም ማህበረሰብን በሙሉ የሚያስደስት ነው ብለውም ያምናሉ፡፡
‹‹ድሮ ስሄድ መኪና አልጠቀምም፤ መኪና እግሬ ነው፣ መሪ ዓይኔ ነው፣ አሁን ላይ መሪዬ ስለተበላሸች ወጣ ብዬ ለመግባት እቸገራለሁ፡፡ ከዚህ ውጪ ግን በህይወቴ ሁሉም ነገር ስለተሳካልኝና እኔን እውቅና ሰጥተው ታሪኬ እንዲቆይ ላደረጉልኝ ሁሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ የማይሞት ታሪክ ተተክሎልኛል›› በማለት የመንገዱ ስያሜ በስማቸው በመሆኑ የፈጠረላቸውን ልዩ ደስታ ገልጸዋል፡፡
‹‹በእርግጥ ስፖርትንና የስፖርት ሜዳን አልጠገብኩም›› የሚሉት አትሌቱ፤ በቅርቡ በተካሄደው የታላቁ ሩጫ ላይ እሳተፋለሁ ብለው ሳይሳካላቸው መቅረቱን ነግረውናል፡፡ ሆኖም አሁንም ከሁለት ኪሎ ሜትር እስከ አምስት ኪሎ ሜትር ድረስ ለመወዳደር ዝግጁ መሆናቸውንም ይገልጻሉ፡፡
‹‹አዛውንቶች መወዳደር በሚችሉባቸው መድረኮች ላይ እሳተፋለሁ፡፡ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ፍላጎቴን አውቆ ሊያሳትፈኝ ይችላል፡፡ በውድድር ቦታ ላይ መገኘት ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ወጣቶችና ለአዛውንቶች ምሳሌ ለመሆን ጅምናስቲክ እየሠራሁና እያሠራሁ ማሳየት እፈልጋለሁ፡፡ የደስታዬ ጫፍም ይህ ነው፡፡ ምክንያቱም እኔና ስፖርት በእጅጉ ተቆራኝተናል፤ ምናልባትም ስፖርት መሥራቴን የማቆመው ከዚህ ዓለም በሞት ስልይ ብቻ ይሆናል፡፡›› በማለትም የወደ ፊት ፍላጎታቸውን ጭምር አብራርተዋል፡፡
‹‹በየጊዜው ስለ እኔ የሚያወሩት የሚዲያ አካላትና ግለሰቦች እንዲሁም ተቋማት ይህንን ክብር እንዳገኝ ስላደረጉኝና የሁሉም ትብብር ስላለበት ምስጋዬ ወደር የለውም፡፡ ሚዲያዎች ድምፅ ባያሰሙልኝ ኖሮ ይህን ሁሉ ዕድል ባለገኘሁ ነበር፡፡ በህይወቴ ኖሬ ሁሉን በማየቴና በመስማቴ ከልብ የመነጨ ምስገና ይድረሳቸው፡፡ መንግሥትም ለሌላው ተምሳሌት የሚሆን ታሪክ ስላሰፈረልኝ እያመሰገንኩት ይህ ቀጣይነት ያለው ተግባር መሆን አለበት እላለሁ፡፡ ይህን ክብር ያላገኙ ሌሎች አንጋፋ ስፖርተኞች እውቅና ሊሰጣቸው ይገባል፡፡›› በማለትም ስሜታቸውን ተናግረዋል፡፡
ጃገማ ዋሚ የክብር ዶክተር አትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ 10ኛ ልጅ ሲሆን፤ ዋሚ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍረካ አትሌቲክስ አባት ናቸው ይላል፡፡
የአባቴን የአትሌቲክስ ህይወት አሁን ስናነሳ የሩጫ ዘመኑ 65 ዓመት ያክል ነው፡፡ በእነዚህ በርካታ ዓመታት በአትሌቲክሱ ጸንቶ ቆይቷል፡፡ እኔ ከዚህ በፊት የእርሱን ልፋትና ጥረት ሌላው ህብረተሰብ እንዲያውቀው አድርጌአለሁ፡፡ መጋቢት 11 እስከ 15 1996 ዓ.ም ‹‹ዋሚና አትሌቲክስ ለግማሽ ምዕተ ዓመት›› በሚል መሪ ቃል፡፡ በአዲስ አበባ ብሄራዊ ሙዚየም ላይ የፎቶ ግራፍ ኤግዚቢሽን አዘጋጅቼ ነበር ይላል፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ ደግሞ ከኢትዮጵያ ሚሊኒየም ጋር አያይዤ በዓለም ላይ ያለ ማቋረጥ ረጅም ጊዜ የሮጠ በማለት ከአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር የዓለም የሳቅ ንጉሥ በላቸው ግርማና አባቴ የተሳተፈበትን የሰባት ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ማዘጋጀት እንደቻለ ገልጾልናል፡፡
ዋሚን ልዩ የሚያደርገው በሁሉም ርቀት የሩጫ ውድድር ላይ መሳተፉ ነው፡፡ 1ሺህ አምስት መቶ ሜትር፣ 3ሺህ ሜትር፣ አምስት ኪሎ ሜትር፣ አስር ኪሎ ሜትር አገር አቋራጭ፣ 21ኪሎ ሜትር፣ 32ኪሎሜትር ሙሉ ማራቶን 42ኪሎ ሜትር ድረስ ሮጧል፡፡ ይህንን ሁሉ መሳተፉ ትልቅ የጥንካሬ መንፈስ ስላለው ነው የሚለው ልጃቸው፤ ትውልዱ እንዲያውቀውና እንዲያስታውሰው በኤግዚቢሽን መልክ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ባለውለታዎች እነማን እንደነበሩ የሚጠቁም መርሀ ግብር ማዘጋጀቱንም ጠቅሷል፡፡ ከእዚህ ጎን ለጎንም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አመጣጥን የሚገልጽና ሻለቃ ዋሚ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በተለያዩ ዶክመንቶች እንዲቀርቡ እንደሚያደርግ ይናገራል፡፡ የዋሚ ጽናትና ትዕግስት ዛሬም ድረስ መኖሩን የሚናገረው ጃገማ፤ እስከ አሁን ድረስ ከስፖርት አለመለየታቸውንና በእዚህ ዕድሜያቸው ለማመን የሚያስቸግሩ ጅምናስቲኮች እንደሚሠሩም ጠቁሟል፡፡
ጃገማ፤‹‹አባቴ በአካል ሲታይ ያረጀ ይምሰል እንጂ አዕምሮው ግን አሁንም አላረጀም፡፡ በእንዲህ አይነት መልኩ ላለ ሰው ደግሞ ክብር መስጠት ከሰውየውም አልፎ ለአክባሪውም ደስታን ይፈጥራል፡፡ ለአንድ ቤት መቆም ወሳኝ መሰረት ነውና መሰረትን ማሰብ ያስፈልጋል፤ ስለዚህ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ ያደረገውን አስተዋጽኦ በመመልከት የተደረገለት ነገር ሁሉ የሚመጥነው ተግባር ነው›› ሲል ያብራራል፡፡
ጃገማ በአባቱ ስም መንገድ መሰየሙን አስመልክቶ የነበረውን ሁኔታ ሲገልጽ፤ ‹‹የአዳማ ከንቲባና አመራሮች ሁሉ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ይህንን የተቀደሰ ሃሳብ በተግባር ማዋላቸው የሚያስመሰግን ሥራ ነው፡፡ መንገዱ በእርሱ ስም መሰየሙ እንደቤተሰብ ሁላችንንም አስደስቶናል፡፡ ከእኛም አልፎ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ የስፖርት ቤተሰቡን ያስደሰተ ተግባርነው፡፡ በእርግጥ መቶኛ ዓመቱ በሚከበርበት ወቅት የአደባባይ ስያሜ እንዲኖር ደብዳቤ ማዘጋጃ ቤት ቀርቦ የነበረ ቢሆንም፣ በአደማ የተደረገው ግን ሳይታሰብ ድንገታዊ ነበረ፡፡ ይህም ምን ያህል ለእርሱ ትልቅ ቦታ እንደሰጡት የሚያሳይ ነው፡፡›› ሲልም ስሜቱን ገልጿል፡፡
‹‹እንኳን ለዜጎቻችን ቀርቶ ለውጭ ዜጎች ስም እየተሰጠ ነው›› የሚለው ጃገማ፤ በተለይ አገር ቤት ውስጥ ያሉና ለአገር ትልቅ ውለታ የዋሉ ሰዎችን ማሰብ ልምድ መሆን እንዳለበት ይመክራል፡፡ የተጀመረው ሥራም እግረ መንገዱን ታሪክን ከማቆየቱ ባሻገር ለባለ ታሪኮች በብርና በቁሳቁስ የማይተመን ደስታን ሊሰጣቸው እንደሚችል ገለጿል፡፡ ተግባሩ ቀጣይነት ኖሮት በሁሉም ቦታ መታወስ የሚገባቸው ባለ ታሪኮች እንዲታወሱበትም መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
የአባቱ ጥንካሬ ብዙ ነገርን ያስተማርው ጃገማ፤ የአባቱን ታሪክ በተቻለው መጠን በምስል በመቅረጽና በጽሑፍ በማዘጋጀት ታሪኩ ሳይሸራረፍና በክብር እንዲቀመጥ እያደረገ ሲሆን፤ ጃገማ እንዳለውም፤ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ድረስ ዋሚ አንድ ምዕተ ዓመት ከአንድ ዓመት አስቆጥረዋል፡፡ ከቤታቸው ወጥተው ያዩዋቸው ሰዎች እስከአሁን በህይወት መኖራቸው ያስገርማቸዋል፡፡ ይህም ለሰዎቹ ልዩ ስሜት ይፈጥራል፡፡ ለእርሱም ቢሆን ጽናትን፣ የአገር ፍቅርን፣ ሰው አክባሪነቱን፣ ሠርቼ አልጠገብኩም ባይነትን እንዲሰርጽበት አድርጓል፡፡ ለጊዜ ዋጋ ከመስጠታቸው የተነሳ የዱሮ ትዝታዎችን የሚናገሩት ቀንን ጠቅሰው መሆኑ ደግሞ ምን ያክል አሁንም ድረስ አዕምሯቸው ብሩህ እንደሆነ ያሳያልም ይላል፡፡
ዋሚ ቢራቱ ታዋቂዎቹን ማሞ ወልዴንና አበበ ቢቂላን አሠልጥነዋል፡፡ ሁሉም ከእርሳቸው የማያልቅ ፍቅርን ተምረዋል፡፡ ትልቅ ተስፋን የሰነቁና ህልማቸውንም ማሳካት የቻሉ የአገር ባለውለታም ናቸው፡፡ ስለዚህ ማንኛውም ሰው በእንዲህ ዓይነት መልኩ በስነ አዕምሮው ዝግጁ ከሆነ ያሰበበት መድረስ ይችላልም ባይ ናቸው፡፡ እነርሱ የአትሌቲክሱ መሰረት ናቸው መልካም ዘርንም ዘርተዋል፡፡የአሁኑ ትውልድ ደግሞ ታሪክ የሠሩና የአገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም መድረክ እንዲውለበለብ ያደረጉትን አርአያ አድርጎ መከተል ይገበዋልም ይላሉ፡፡
ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ ስድስት ወንዶችን አምስት ሴት ልጆችን ወልደዋል፡፡ ከእነዚህም 27 የልጅ ልጅ እና 20 የልጅ ልጅ ልጅ ማየት ችለዋል፡፡እርሳቸው አሁን ጡረተኛ ናቸው፡፡ የዓይንና የጆሮ ችግር ካልሆነ በቀር ጤንነታቸው የተጠበቀ ነው፡፡ በእርሳቸው ውስጥ ያለው ጥንካሬ ግን ጡረታ አልወጣሁም እያስባላቸው ነው፡፡ ጡረታ ከወጡ በኋላም ልጆችን በማማከር፣ በማሰልጠንና በማወዳደር እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
ዝግጅት ክፍሉም በህይወት ያሉ እንቁዎቻችንን ካለፉ በኋላ መዘከሩ እንዳለ ሆኖ በህይወት እያሉ ማስታወስና እውቅናመስጠት ከገንዘብ ይልቅ ትልቅ የመንፈስ እርካታ ስላለው፤ ይህ ዓይነቱ ተግባር በሌሎችም አካባቢዎች ቢሰፋና ቢደጋጋም ለሌላው ተነሳሽነትን ይፈጥራል እንላለን፡፡
ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ በተለያዩ የሩጫ መድረክ ላይ አገራቸውን ያስጠሩ ድሎችን ያስመዘገቡ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል በ1ሺ500፣ 3ሺ፣ 5ሺ፣ 10ሺ፣ 21ኪሜ፣ 25ኪሜ፣ በ32ኪ.ሜ በአገር አቋራጭ እና የተለያዩ የማራቶን ውድድሮች ላይ በመሳተፍ 51 የወርቅ፣ 44 የብር እና 30 የነሐስ ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችለዋል፡፡ 21 ሰርተፍኬት፣ 4 ዲፕሎማ እና ከ40 በላይ ዋንጫዎችን ወስደዋል። በተለያየ ወቅትም የኢትዮጵያ ባንዲራ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አስችለዋል። የሶምሶማ ሩጫ በአገራችን እንዲለመድ ለማድረግ ጥረት ማድረጋቸውም በታሪካቸው ተቀምጧል፡፡

Published in ስፖርት

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለ17 ቀናት ያካሄደውን ስብሰባ አስመልክቶ የተሰጠውን የማጠቃለያ ማብራሪያ በተከታታይ አቅርበናል፡፡ በዛሬው እትማችን የደኢህዴንና ኢህአዴግ ሊቀመንበር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ማንነትን በተመለከተ እንዲሁም በአገሪቱ ሰላም በማስፈን ሂደት ተዋንያን ለሆኑ አካላትና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሊኖራቸው በሚገባው አስተዋፆኦ ላይ ያስተላለፉትን መልክዕት ይዘን ቀርበናል፡፡
የደኢህዴንና ኢህአዴግ ሊቀመንበር አቶ ኃይለማርያም ማንነትን አስመልክቶ እንዳብራሩት እያንዳንዱ ሰው እኔ የዚህ ብሔር ተወላጅ መሆን አለብኝ ብሎ ወዶ፣ መርጦ፣ ፈቅዶ የተወለደበት ጉዳይ አይደለም። ነገር ግን ማህበራዊ ግንኙነቱ በአንድ ብሔር ውስጥ ማንነቱ የሚገለጽበት፣ የቡድን ሥርዓቶች ተፈጥረዋል። ከዚህም ተነስቶ በቋንቋ፣ በባህልና በመሳሰለው የሚገናኝ ሰው ብሔሩ፣ ኅብረተሰቡ በአንድነት የሚስተናገዱበት የራሱ ሥርዓት በባህልም በታሪክም ስላለው ነው። ይህ ያለውን፣ በተፈጥሮ የተሰጠውን ነገር እንዳልነበረ እንዳልሆነ አድርጎ ለመካድ የሚደረግ ጥረት ትክክል አይደለም፤ ይህንን ደግሞ ሕዝቦች ማንነታቸውን ለማረጋገጥ ሲሉ የተለያዩ ትግሎች አድርገው የተጎናጸፉት ድል ነው።
ሌሎች ብሔሮች ጋር ሆነው ደግሞ፥ ክልልም ሆነ አገር ሊሆን ይችላል፤ አንድ ደግሞ የተለየ ፖለቲካ ማኅበረሰብ ሲፈጥሩ፥ ከዚህ ተጠቃሚ መሆናቸውን አረጋግጠው ነው። በኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ታሪካቸው ወደኋላ በሚታይበት ጊዜ መስተጋ ብራቸው ጠንካራ የነበረ፤ በተለያዩ አጋጣሚዎች፥ ዛሬ ሁላችንም እንድንኮራ የሚያደርጉ፤ ኢትዮጵያዊ ማንነታችንም ላይ ከፍተኛ ስሜት የሚፈጥሩ በጋራ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የሠሯቸው ታሪካዊ ገድሎች አሉ። ዛሬ እኔ አንድ የኢትዮጵያ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኜ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በምሄድበት ጊዜ የአደዋ ድል እየተነሳ «እናንተኮ የጥቁር ሕዝቦች ነፃነት ተምሳሌት ናችሁ፤ ኢትዮጵያውያን፤ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ይህን ሠርታችኋል» ተብሎ ሲነገር ኢትዮጵያዊ ማንነቴ ምን ያህል እንደምኮራበት ሁላችን የምናውቀው ነው።
ስለዚህ ይህ ማንነታችን፤ ጠንካራ ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ወደፊትም አንድ የጋራ እሴታችን ሆኖ የሚቀጥል ይሆናል። ይህን ደምስሶ ለመሄድ የሚሞክር ማንኛውም ዓይነት ሁኔታ ትክክል እንዳልሆነ ታውቆ ይሄ የጋራ ግንኙነታችን፤ እሴታችን እንዲጎለብት። በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ ግንኙነታችን የሻከሩባቸው ጉዳዮች ደግሞ እንዲስተካከሉ በሚያደርግ አንድነት እንዲመሰረት ነው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሲጀመር ቃልኪዳን የገቡት።
ስለዚህ ብሔራዊ ማንነታቸው ለኢትዮጵያዊ አንድነታቸው ትልቅ መሠረትና ጠንካራ አንድነት የሚፈጥር፤ መስተጋብሩንም የሚያጠናክር ነው የሚሆነው የሚለው ሊሰመርበት ይገባል። እዚህ ላይ አንድ ነቀርሳ ሊሆን የሚችለው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን በመካድ አክራሪ ብሔርተኝነት ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ በሚኖርበት ጊዜ ይህንን መስተጋብራችንንና ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ያፈርሳል።
ስለዚህ ኢህአዴግም በአጠቃላይ በአገራችንም ዴሞክራሲያዊ አንድነት ነው፤ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ነው ለእኛ ትልቁ ጠቃሚ ብሎ አስምሮ የወሰደበት ሁኔታ አለ። ስለዚህ ይህን ጥያቄ የሚያነሱ አካላት አክራሪ ብሔርተኝነት በሚነግስበት ጊዜ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ሊንድ ይችላል የሚለው ትክክል ነው። ስለዚህ አክራሪ ብሔርተኝነትን መዋጋት አለብን፤ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነታችንን ማጎልበት አለብን። በመፈቃ ቀድና በጋራ አንድነት ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊነት ማጎልበት አለብን። ይህ ኢትዮጵ ያዊነት ዛሬም የተፈጠረ ባይሆን ነገር ግን ሻካራ ግንኙነቶችን እያረምን ጠንካራውን እያበለጸግን አንድነታችንን ማጠንከር አለብን።
ዛሬኮ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ ካሉ አገሮች ውስጥ በሁለተኛ ደረጃ ትልቅ የሕዝብ ብዛት ያላት አገር ናት ተብሎ ብዙ ኢንቨስተሮች ወደአገራችን ሊመጡ የሚፈልጉበት ዋናው ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጠንካራ አንድነት በመፍጠራቸው ነው። ባይሆን ኖሮ እኛ ተከፋፍለን ትንንሽ አገሮች ብንሆን ይህን ዓይነት ዕድል አናገኝም። ስለዚህ የጋራ ተጠቃሚነታችንን ስለምናውቅ ነው ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ጠንክሮ እንዲወጣ የምንፈልገው።
ኢትዮጵያዊ አንድነታችን የበለጠ በዓለም አቀፍ ውድድርም፤ አሁን የዓለም ትስስር በጣም በበረታበት ሁኔታ ተበታትኖ ትንንሽ አገር ሆኖ የተጠቀመ አገር እንደሌለ አውቀን እኛ ኢትዮጵያዊ አንድነታችን መጠናከር አለበት። ይሄ መሠረት ስላለው በዚህ መሠረት ላይ መገንባት አለብን ብለን የምንወስደውም ከዚህ ተነስተን ነው። ትልቅ ገበያ፤ ትልቅ አምራች፣ ትልቅ ተወዳዳሪ በሚኮንበት ጊዜ ከተበጣጠሰ ኃይል ይልቅ የበለጠ ተጠቃሚ እንሆናለን በሚል ታሳቢ ነው። እና የበፊቱ ብቻ ሳይሆን የወደፊቱም ቢሆን አንድነታችን ተጠናክሮ መሄድ ስላለበት ለዚህ አንድነት የሚሆኑ የጋራ መግባባቶችን ይበልጥ ማጎልበት ይገባናል የሚል አቅጣጫ ተቀምጧል።
ለምሳሌ በትምህርት ሥርዓታችን እንኳ ብናይ፥ የትምህርት ሥርዓታችን ይሄ ኢትዮጵያዊ አንድነታ ችንን፤ ልጆቻችን ጠንክረው እንዲይዙ ሊያደርግ የሚችል መሆን አለበት። አሁን በትምህርት ሥርዓ ታችን ውስጥ ልጆቻችንን ስንቀርጽ ስለኢትዮጵያዊ አንድነታችንም ጭምር፤ ስለታላ ቅነቷ፥ ስለ ሕዝቧ ብዛት፣ ስለታሪኳ መናገር አለብን። የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች ታሪክ ተሰብስቦ አንድ ጠንካራ አገር እንድትሆን ያደርጋታል።
ይህን ሁሉም መጋራት አለበት። በትምህርት ሥርዓታችንም ይህን የሚያጋራ ሁኔታ መፍጠር ይገባናል። ስለዚህ ጠንካራ በዓለት ላይ የተመሠረተ ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ለማጎልበት የሚያስችል መሠረት ስለተጣለ በዚህ ላይ ስንገነባ ያሉ ጉድለቶቻችንን የበለጠ ማጠንከር ይገባናል።
አቶ ኃይለማርያም በአገሪቱ ሰላም በማስፈን ሂደት ተዋንያን ለሆኑ አካላትና ለመላው የኢትዮ ጵያ ሕዝቦች ሊኖራቸው በሚገባው አስተዋፅኦ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የአራቱም የኢህአዴግ የየብሔራዊ ድርጅቱ ሊቃነ መናብርት አንድ ላይ ሆነው ለሀገራቸው ሕዝቦች ይቅርታ በጠየቁት መሠረት በሥራና በተግባር ለማካካስ መዘጋጀ ታቸውን አስታውቀዋል፡፡ አሁንም በድጋሚ እኛ ሥራ አስፈፃሚውን ወክለን እዚህ የተገኘን አመራሮች ሕዝባችንን ከፍተኛ የሆነና የከበረ ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡ ይቅርታውንም ደግሞ በተግባር ለማሳየት መቁረጣችንን እንገልፃለን፡፡
ዋናው ጉዳይ እኛ በውስጣችን ያካሄድነው ግምገማና የፈጠርነው ትልቅ መግባባት እና የአመለካከትና የአስተሳሰብ አንድነት የተግባር አንድነት መነሻ ይሆነናል ብለን በሙሉ ልባችን እንተማመናለን፡፡ ይሄን ይዘን በፍጥነት ሊፈቱ የሚገቡ ሕዝባችን የተጎሳቆለባቸው በተለይም ድግሞ ግጭቶች በተከሰቱባቸው አካባቢዎች ላይ ያጋጠሙንን ችግሮች ቶሎ ለመፍታት ከወዲሁም ሥራ ጀምረናል፡፡ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን ፈጥነን ለማቋቋም የሚያስችል ሥራ አሁን ጀምረናል፡፡
ይህንን ወደታች ወርደንም እኛ እንደአመራርም ከሕዝቡ ጋር ሆነን ፈጥንን ለመፍታት እንሰራለን፡፡ ከዚህም በላይ በግጭቱ ወቅት ሕገወጥ ተግባር የፈፀሙ ወገኖችን በሕግ ለመጠየቅ የሚያስችሉ ሥራዎችንም እንደዚሁ አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ሕዝቦቻችን በግጭቱ አካባቢዎች ላይ በተለይም ኦሮሚያና ሶማሌ ክልል ወስን አካባቢ ያለው ሕዝብ ለበርካታ ጊዜያት በዚህ ጭንቅት ውስጥ የቆየና የተጎዳ እንደሆነ እናውቃለን፡፡
በአካባቢው ያለው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሀገር ሽማግሌዎችም የሃይማኖት አባቶችም ወጣቶችም ሴቶችም የጀመሩትን ሥራ እኛም እንደ አመራር ይሄን ማስተባበራችንን የበለጠ ማጠናክር ይገባናል፡፡
በአጠቃላይ የሀገራችን ሕዝቦች ግንኙንት እንዲጠናከር የተጀማመሩ ሥራዎች አሉ፡፡ በአጎራባች ክልሎች ላይ ያሉ ሕዝቦች መገናኘታ ቸው ብቻ ሳይሆን፣ ሀገራዊም ሆኖ ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን በሚያጠናክር መንገድ ህብረታችንን በሚያጎለብት መንገድ ለመስራት አቅደናል፡፡ በዚህም ላይ ሕዝቡ በሰፊው እንዲሳተፍ እንፈል ጋለን፡፡
የሀገራችን ምሁራንም በሀገራችን በምናካሂደው የሰላም፣ የልማት፣ የዴሞክራሲ ግንባታ ሥራዎች ወቅት ኢህአዴግ አሁን ከገባብት አጣብቂኝ ውስጥ ወይም ችግር ውስጥ ለመውጣት ራሱን ባዘጋጀበት በዚህ ወቅት የበኩላቸውን ምሁራዊ ሚናቸውን መጫወት ይገባቸዋል፡፡
እንግዲህ የአንድ ሀገር እድገት እየፈጠነ ሲሄድ የተለያዩ ውስብስብ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮችም እንደሚያጋጥሙ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት በጥናትና በምርምር በተለያዩ ሞያዊ ጥበቦች በመታገዝና ነው፡፡ ለዚህም ምሁራን ብቻ ሳይሆኑ የኪነ ጥበብ፣ የሥነ ጥበብና ሥነ ጽሑፍ ሞያተኞችም የራሳቸውን በጎ አስተዋፅኦ ማበርከት ይችላሉ፡፡ እነዚህም የኅብረተሰብ ክፍሎች የራሳቸውን ከፍተኛ ሚና መጫወት ይገባቸዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋሞቻችንም የሀገራችን የመቻቻ ልና አብሮ የመኖር ተፈቃቅዶ በጋራ የማደግ ጉዳይ ይመለከታቸዋል፡፡ እስካሁንም ድረስ የራሳቸውን አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ ቆይተዋል፡፡ ስለዚህ በዚህም ዙሪያም የራሳቸውን የማይተካ ሚና መጫውት እንዲቀጥሉ እንፈልጋለን፡፡
ወጣቶቻችን አሁን በሀገሪቱ በሚስተዋለው ችግር ዋነኛዎቹ ተጎጂዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ወጣቶቻችንን አዳምጠን ለመረዳት ጥረት እናደርጋለን፡፡ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥያቄያቸው በአግባቡ እንዲመለስ አቅም በፈቀደ መጠን የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን፡፡
ይህ ጉዳይ ደግሞ ከወጣቶቹ ሙሉ ተሳትፎ ውጪ ሊካሄድ አይችልም፡፡ ጥያቄዎቻቸውንም በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ ማቅረብ ይጠበቅባ ቸዋል፡፡ እስካሁን ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያደረጉትን አስተዋፅኦ የበለጠ ማጠናከር ይኖርባቸዋል፡፡ እኛ ዴሞክራሲን የሚያቀጭጩ ችግሮችን ለመፍታት በተዘጋጀንበት በዚህ ወቅት ወጣቶቻችን የራሳቸውን ዴሞክራሲያዊ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ ማቅረብ እንፈልጋለን፡፡
በአጠቃላይ ሴቶች፣አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች እና ሌሎች የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ጨምሮ መላው የሀገራችን ሕዝቦች ሰላም ዴሞክራሲና ልማት ይፈልጋሉ፡፡ ይህንን ለማሳካት ቆርጠን ተነስተናል፡፡
በለውጥ ጉዞ ላይ እንገኛለን፡፡ በለውጥ ሂደት ውስጥ ሆነን ግን እነዚህ ችግሮች አጋጥመውናል፡፡ በእኛ እምነት ሁላችንም ቆርጠን ከተነሳን ይሄ ጊዜያዊ ችግር ሆኖ ሊገለበጥ እንደሚችል እናም ናለን፡፡ ስለዚህ ለዚህ በጋራ እንድንሰለፍ አሁንም በድጋሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላትም ጭምር እንደዚሁ የጀመርነውን የመድብለ ፓርቲ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለማጎልበት መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ ዙሪያ ያሉትን ችግሮች ነቅሰን አውጥተን ለመፍታት በቁርጠኝነት ላይ ተመርኩዘን በጋራ መስራት ይኖርብናል፡፡ ሀገራችን የዳበረ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ሥርዓት ባለቤት እንድትሆን ሁላችንም የበኩላችንን ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ሚና እንድንጫወት በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
በአጠቃላይ የድርጅታችን ጉዞ አባሎቻችን ካድሬዎቻችን የሥራ አስፈፃሚውን መንፈስ በመላበስ ለሕዝቡ በተለይም የመንግሥት መዋቅሩ የሚሰጡት አገልግሎት ወሳኝ ነው፡፡ ከዚህ አኳያም ሕዝቡን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል እንዲቻል ለመንግሥት መዋቅሩም እንደዚሁ ጥሪ ለማቅረብ እንፈልጋለን፡፡
በተግባር ሂደት ውስጥ አሁንም ከችግር ነፃ የሆነ አልጋ በአልጋ ጉዞ ይኖራል ብለን አናምንም፡፡ ችግሮችን ተጋፍጠንና ፊትለፊት ተዋግተን ለማሸነፍ ቁርጠኝነታችንን እንገልጸለን፡፡ በዚህ በተለይ በታዳጊ ኢኮኖሚ በሽግግር ሂደት ውስጥ ባለ ሀገር ከችግር ነፃ የሆነ ጉዞ ይኖራል ብለን በጭራሽ አናምንም። ነገር ግን ችግሮቻ ችንን ተጋፍጠን እንዳናሸነፍ ወደኋላ የሚጎትቱ ነገሮችን በጣጥሰን ይህንን ድል ለመጎናፀፍ መጓዝ ይኖርብናል፡፡
ስለዚህ በአጠቃላይ ኢህአዴግ አሁን ባለው የሥራ አስፈፃሚ ዘንድ የተፈጠረው አመለካከትና አንድነት ለሥራ በጣም የሚያነሳሳ ደረጃ ላይ መሆኑን በድጋሚ እየገለፅኩ መልካም ትብብራችሁ እንዳይለየን አደራ ለማለት እፈልጋለሁ፡፡ አመሰግ ናለሁ፡፡

Published in ፖለቲካ

የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የተፈጥሮ ሀብቶችን በዘላቂነት በመጠቀም የዜጎችን የኑሮ መሠረትና የአገርን ኢኮኖሚ እድገት በአስተማማኝ መሠረት ላይ ለመገንባት ሚናው የጎላ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ኢኮኖሚያቸው በግብርና ላይ ለተመሰረተ አገራት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የክፍለ-ኢኮኖሚው የህልውና መሠረት ይሆናል፡፡ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ በተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች የተመዘገቡ ውጤቶች አገሪቱ ለማሳካት ላቀደችው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ግብዓት በመሆን አገልግለዋል፤ እያገለገሉም ይገኛሉ፡፡
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ እንደተጠቀሰው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራዎችን ውጤታማ ማድረግ ዋነኛ የምርትና ምርታማነት ማሳደጊያ ስልት ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት ከሀገሪቱ አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር አብላጫውን የሚወክለውን አርሶ አደር በተፋሰስ ልማቱ ዋነኛ ተዋናይና የሥራው ባለቤት እንዲሆን በማስቻል ሰፊ ሥራዎች እንደተሰሩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የተገኘው ውጤት ቀላል የማይባልና ለበርካታ ሀገራትም በምርጥ ተሞክሮነት እየቀረበ ያለ ቢሆንም አሁንም ብዙ መስራትነና መትጋትን እንደሚጠይቅ እነዚሁ መረጃዎች ጨምረው ይጠቁማሉ፡፡
የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ በአገሪቱ ላለፉት ዓመታት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ የዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራም ጥር 1 ቀን 2010 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ ተጀምሯል፡፡ በዕለቱ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ሥራው በይፋ ተጀምሯል፡፡ ሌሎቹ ክልሎችና አካባቢዎችም በዕለቱ አልያም ራሳቸው ባስቀመጡት ጊዜ መሠረት ሥራውን ማከናወን ይጀምራሉ፡፡ ለ2010 ዓ.ም የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ የተደረጉ ዝግጅቶችንና የትኩረት አቅጣጫዎችን አስመልክቶ በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ ከሆኑት ከአቶ ዓለማየሁ ብርሃኑ ጋር ያደረግነውን ቃለ-ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
የዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ አጠቃላይ ገፅታ
በዘንድሮው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ላይ ከ10 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለሥራውም 6700 የሚሆኑ የተፋሰስ ልማት ቦታዎችም ተለይተዋል፡፡ሥራው በሁሉም ክልሎች ይካሄዳል፡፡
የዘንድሮውን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ባለፉት ዓመታት ከተከናወኑ ሥራዎች ለየት የሚያደርጉት ነገሮች አሉ፡፡ ከነዚህም መካከል አንዱ ጥራትን ማዕከል ላደረገ ሥራ ትኩረት መሰጠቱ ነው፡፡ መረጃዎችን የማጥራት ሥራም ሌላው ተግባር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ የተሰሩ ሥነ-አካላዊና ሥነ-ሕይወታዊ ሥራዎችን በተጠናከረ መልክ የመንከባከብና ውጤታማ በሆነ መልኩ ተግባራዊ የማድረግ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ ይከናወናል፡፡ የሚሰሩ ሥራዎችንም በሥነ-ሕይወታዊ ዘዴዎች በማጠናከር የሥራውን ዘላቂነት ለመጠበቅ እቅድ ተይዟል፡፡
የትኩረት ማዕከላት
የዘንድሮው ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ዋና የትኩረት ማዕከሉ ጥራት ነው፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት የተከናወኑት ሥራዎች ብዙ ውጤቶች የተገኙባቸው ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ሥራዎቹ ከተሰማራባቸው የሰው ኃይል አንፃር ሲታይ ጥራታቸው የተጓደሉባቸው ሁኔታዎች ተስተውለዋል፡፡ ለአብነት ያህል በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው ወቅት የተሰሩ እርከኖች የመፈራረስና የመደፈን እንዲሁም የሚተከሉ ችግኞች በተፈለገው መጠን አለመጽደቅ ችግሮች ታይተዋል፡፡ ስለሆነም በዘንድሮው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ለእነዚህ ችግሮች ዘላቂ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች እንዲሰሩ እቅድ ተይዞ እየተተገበረ ይገኛል፡፡
የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው ሳይንሳዊነት
የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራውን በሳይንሳዊ መንገድ ለማገዝ በተለይም ደግሞ በሥነ-ሕይወታዊ ዘዴዎች ለማጀብ የሚደረጉ ጥረቶች አሉ፡፡ የአቅም ግንባታ ሥራዎች በስፋት ይስራሉ፡፡ ሥራዎቹን በሳይንሳዊ ዘዴዎች የተደገፉ ማድረጉ እንደተጠበቀ ሆኖ አርሶ አደሩን ጨምሮ በክልልና በፌደራል ደረጃ ያሉ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ይህም እውቀትን ማዕከል ያደረገ ሥራ እንዲሰራ ለተያዘው እቅድ መሳካት ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡ ይህም ቀጣይነትም ይኖረዋል፡፡
የሴት አርሶ አደሮች ተሳትፎ
በዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የሴት አርሶ አደሮችን ተሳትፎ ለማጉላት የታቀዱ ሥራዎችም አሉ፡፡ በተፋሰስ ልማት ሥራዎች ላይ ከሚሳተፉት አርሶ አደሮች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡ ከባለፉት ዓመታት ያለው ተሞክሮ እንደሚያሳየውም፣ በጥራትም ሆነ በብዛት ውጤታማ መሆን የተቻለባቸው አካባቢዎች ሴቶች በራሳቸው አደረጃጀቶች የሰሩባቸው ናቸው፡፡
እነዚያን በጎ አፈፃፀሞች በመቀመርም ለዘንድሮው ሥራ ጥሩ ግብዓት እንዲሆኑ የቀደሙትን ዓመታት ሥራዎች ልምድ ለመውሰድ ታቅዷል፡፡ ከዚህ አንፃር የሴት አርሶ አደሮችን ተሳትፎ በማሻሻልና ባለፉት ዓመታት በተከናወኑት የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የነበራቸውን ጠንካራ አፈፃፀም በማጎልበት በዘንድሮው ሥራም ይህንን አፈፃፀማቸውን እንደሚያጠናክሩ ይጠበቃል፡፡
ከባለፉት ዓመታት ሥራዎች የተገኙ ልምዶች
ቀደም ባሉት ዓመታት የተከናወኑት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች ለዘንድሮው ሥራ የሚያበረክ ቷቸው አስተዋፅኦዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ዓመታት የተቀመሩ ልምዶችም አሉ፡፡ እስካሁን ከተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች የተገኙ ውጤቶች ብዙ ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል ተራቁተው የነበሩ መሬቶች መልሰው አገግመዋል፤ ገላጣ ተራሮች በእፅዋት ተሸፍነዋል፤ ለአራዊት መጠለያነት ከማገልገላቸውም ባሻገር የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ የደረቁ ምንጮች ጎልብተው ለሰውና ለእንስሳት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፤ የወንዞችን የውሃ መጠን/አቅምም ለመጨመር አግዘዋል፡፡ ሌሎች የተገኙ ውጤቶችም አሉ፡፡ እነዚህ ውጤቶች በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በስፋት የታዩ/የተገኙ ናቸው፡፡ እነዚህ መልካም ተሞክሮዎችና ልምዶች ለዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ጉልበት/ግብዓት የሚሆኑ ናቸው፡፡ አርሶ አደሮችም ሥራዎቹንና ውጤቶቹን በጉልህ ያዩዋቸው ስለሆኑ ለሥራው ግፊት/ቀስቃሽ አያስፈልጋቸውም፡፡
ሥራውን ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ የተያዙ እቅዶች
እስካሁን ያለው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ እየተሰራ ያለው በዘመቻ መልክ ነው፡፡ ሥራው ብዙ ውጤቶች የተገኙበትና ልምዶች የተቀመሩበት በመሆኑ ሥራውን በዘመቻ መልክ ማስቀጠሉ የሚመከርና የሚደገፍ አይደለም፡፡ በመሆኑም የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራውን ዘላቂና አስተማማኝ (Sustainable) ለማድረግ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ መደበኛ ሥራ ሆኖ በእያንዳንዱ አርሶ አደር በቋሚነት የሚከናወን ተግባር መሆን አለበት፡፡ የሥራው ዘላቂነትና አስተማማኝነት ዋስትና የሚኖረው እያንዳንዱ አርሶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር በባለቤትነት ይዞት በቋሚነት ሲሰራው በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራል፡፡ ከገጠሩ ነዋሪ በተጨማሪ የከተማ ነዋሪውም ጭምር የተፋሰስ ልማት ሥራን መደበኛ ሥራ አድርጎ በማየት ተፈጥሮን ጠብቆ መኖር እንደሚገባ ታምኖበትም በትኩረት መሰራት ይገባዋል፡፡ በዚህም ሥራው ዘላቂና አስተማማኝ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያደርጉ የትኩረት አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል፡፡
ሊያጋጥሙ ይችላሉ ተብለው የሚጠበቁ ችግሮችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች
የዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ሲከናወን ሊያጋጥሙ ይችላሉ ተብለው የሚጠበቁ ችግሮች/ መሰናክሎች ይኖራሉ፡፡ ከነዚህም መካከል የመረጃ እጥረቶችና እንዲሁም የጥራት ክፍተቶች ሊኖሩ/ ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ ለዚህም ሥራው በክልሎች ከፍተኛ አመራሮች የሚመራ በመሆኑ ችግሮቹ እየተለዩና እየተጣሩ ትክክለኛ መረጃዎች እየተሰጡ ሥራውን ማከናወን እንደሚገባ ሁሉም ክልሎች የጋራ አቋም ይዘዋል፡፡ በሌላ በኩል በቂና ተመጣጣኝ የሥራ መሣሪያ አቅርቦት ክፍተት ተፈጥሮ የሚሰማራው የሰው ኃይል (ጉልበት) እንዳይባክን ስጋቶች አሉ፡፡ ከዚህ አንፃርም እያንዳንዱ ሰው በየግሉ የሥራ መሣሪያ እንዲይዝ ለማድረግ የሚያስችል ትኩረት እንዲሰጥ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ የፀጥታ ችግሮች በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው ላይ አሉታዊ ጫና እንዳያሳድር የሚል ስጋት በመኖሩ አርሶ አደሩ በችግሮቹ ምክንያት ሥራው መስተጓጎል እንደሌለበት ከዚህ ቀደም ልምዶቹ በመነሳት በተነሳሽነት በሥራው ላይ እንዲሰማራ የትኩረት አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
የሚጠበቁ ውጤቶች
የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ዋና ግቡ የምርትና ምርታማነት እድገትን ማስቀጠል ነው፡፡ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የግብርና ሥራዎችን የሚያሳልጡ ናቸው፡፡ በሌላ በኩልም ሥራዎቹ ምርትና ምርታማ ነትን በማሳደግ የምጣኔ ሀብቱን መዋቅራዊ ሽግግር የሚያግዙ ናቸው፡፡ ስለሆነም በአጠቃላይ ከዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የአገሪቱን ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ ተግባራት ይጠበቃሉ፡፡
በሥራው ላይ ሁሉም አርሶ አደሮች፣ ከፊል አርብቶ አደሮችና ባለሙያዎች በጥራት ላይ ባተኮረው የዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

ኳታር የባህረ ሰላጤው ፖለቲካዊ ውዝግብ መፍትሄ እንዲያገኝ ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች ጣልቃ ገብተው በሳዑዲ አረቢያ ከሚመራውና ማዕቀቦችን ከጣለባት የሀገራት ጥምረት ጋር እንዲያደራድሯት ጥሪ አቅርባለች፡፡ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰሞኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኳታርና በሌሎቹ የባህረ ሰላጤው አገራት መካከል የተፈጠረው ፖለቲካዊ ውዝግብ በቀጣናው ሕዝብ ላይ አሉታዊ ላይ ጫናዎችን እያሳደረ እንደሚገኝ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ በሰጠው መግለጫ፣ አገሪቱ ውዝግቡ መፍትሄ እንዲያገኝ ለማድረግ ዓለም አቀፍ ተቋማትን በአማራጭነት ለመጠቀም እንቅስቃሴ እንጀመረች አስታውቋል፡፡
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሉልዋህ አል-ኻቴር በዶሃ በሰጡት መግለጫ፣ ውዝግቡ መፍትሄ እንዲያገኝ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶችና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት በጉዳዩ ጣልቃ ገብተው እንዲያደራድሯቸው መንግሥታቸው እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግ ረዋል፡፡
እ.አ.አ በኅዳር 2017 ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛው ኮሚሽን የተላኩ ተወካዮች ኳታርን ጎብኝተው ከ20 በላይ ከሚሆኑ መንግሥታዊና የሲቪል ማኅበራት እንዲሁም ፖለቲካዊ ቀውሱ ተፅዕኖ ካሳደረባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተው ነበር፡፡ የኮሚሽኑ ቡድንም ለአንድ ሳምንት በቆየ ጉብኝቱ የታዘባቸውን ጉዳዮች ያጠናቀረበትን ሪፖርት ለኳታር ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ ልኳል፡፡
«ገለልተኛና ዓለም አቀፍ ዕይታ ባለው ተቋም የተጠናቀረው ሪፖርት ጠቃሚ ነጥቦችን በማንሳት ብዙ ጉዳዮችን አሳይቷል፤ ውዝግቡ እልባት እንዲያገኝ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጉዳዩን እንዲያዩት ለማድረግ ጥረት እያደረግን ነው፤ ሁሉም አማራጮች በእጃችን ላይ ናቸው» በማለት ተናግረዋል፡፡
የኳታር ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ ሊቀ-መንበር አሊ ቢን ስማኽ አል-ማሪ በበኩላቸው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛው ኮሚሽን ቡድን ይፋ ያደረገው ሪፖርት በኳታር ላይ የተጣሉት ማዕቀቦችና የተወሰዱት እርምጃዎች ሕገ-ወጥ እንደሆኑ አሳይቷል ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እርምጃዎቹ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያስከትሉ የዘፈቀደ ድርጊቶች እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡
እንደሊቀ-መንበሩ ገለፃ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛው ኮሚሽን ቡድን ሪፖርቱን ይፋ ከማድረጉ በፊት በኳታር ላይ ማዕቀብ ወደጣሉባት አገራት ጉብኝት ለማድረግ ጥያቄ አቅርቦ ምንም ዓይነት ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ የአልጀዚራው ዘጋቢ መሐመድ ቫል ከዶሃ ባሰራጨ ው ዘገባ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛው ኮሚሽን ቡድን ይፋ ያደረገው ሪፖርት ለሰብዓዊ መብቶችና ፖለቲካዊ ቀውሱ አሉታዊ ተፅዕኖ ላሳረፈባቸው ኳታራውያንና በአገሪቱ ውስጥ ለሚገኙ የውጭ አገራት ዜጎች እንደ ትልቅ ድል እንደተቆጠረ ገልጿል፡፡
በኳታር ላይ የተወሰዱት እርምጃዎች ኳታራውያንን ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የማዕቀቡ ጣይ አገራት ዜጎችንም ጭምር አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ ሪፖርቱ ማመላከቱን ዘጋቢው ተናግሯል፡፡
በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው የአገራት ቡድን በኳታር ላይ የጣለባት ማዕቀቦች እጅግ አስከፊ ናቸው ሲል የኳታር ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ በተደጋጋሚ ቅሬታና ክስ ማሰማቱ ይታወሳል፡፡ ማዕቀቡ ለወትሮው እንደልባቸው ይገናኙ የነበሩት የኳታርና የማዕቀብ ጣዮቹ አገራት ዜጎች እንዳይገናኙና እንዳይተያዩ በመከልከሉ «እርምጃው ከበርሊን ግንብ የባሰ ነው» ሲሉ የኮሚቴው ሊቀ-መንበር አሊ ቢን ስማኽ አል-ማሪ መግለፃቸው የሚታወስ ነው፡፡
የኮሚቴውን ቅሬታና ክስ ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶችም ደግፈውታል፡፡ ለአብነት ያህል አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ባለፈው ሰኔ ባወጣው መግለጫ፣ በኳታር ላይ የጣሉት አገራት በሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ላይ እየተጫወቱ እንደሆነ ገልፆ ነበር፡፡
«የሪፖርቱ ግኝት እንደሚያመለክተው ከኳታር በተቃራኒ ተሰልፈው በኳታር ላይ ማዕቀብ የጣሉባት አገራት የወሰዷቸው እርምጃዎች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን የማቋረጥ ተግባራትና ምጣኔ ሀብታዊ ማዕቀቦች ብቻ ተደርገው ሊታዩ አይችሉም፤ እርምጃዎቹ በኳታር ዜጎችና በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ የውጭ አገራት ዜጎች ላይ አደጋን የደቀኑ ሕገ-ወጥ፣ ክብረ ነክ፣ ወገንተኛ፣ በዘፈቀደ የተወሰኑ ናቸው» በማለት እርምጃዎቹ ከኢኮኖሚ የዘለለ ትርጉም ያላቸው እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የኩዌት ኢሚር ሸክ ሳባህ አል-አህመድ አል ሳባህ ኳታርና ሌሎቹ የባህረ ሰላጤው አገራት የገቡበት ፖለቲካዊ ውዝግብ ካልተፈታ ለቀጣናው ሰላም ከባድ አደጋ እንደሚ ደቅን አስጠንቅቀዋል፡፡ ኢሚሩ ሰሞኑን ለሁለት ቀናት ያህል በኩዌት በተካሄደው የባህረ ሰላጤው ትብብር ካውንስል ጉባኤ ላይ ባሰሙት መልዕክት፣ ኳታርና ሌሎቹ የባህረ ሰላጤው አገራት ቅራኔያ ቸውን በአፋጣኝ እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ «ቀጣናውን መልካም ያልሆኑ ነገሮች እየተፈ ታተኑት ይገኛሉ፤ በመካከላችን ያሉትን ልዩነቶች በመፍታት አንድነታችንን ማጠናከር ይገባናል» በማለት ኳታርና ሌሎቹ የባህረ ሰላጤው አገራት የገቡበት ፖለቲካዊ ውዝግብ ለቀጣናው ሰላም አሉታዊ ሚና እንዳለው በአንክሮ ገልጸዋል፡፡
በአረብ ባህረ ሰላጤ ቀጣና ኃያል ናት የምትባለውን ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ ግብፅ፣ ባህሬንና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች «ኳታር አሸባሪዎችን እየደገፈች ነው፤ የነሳዑዲ ባላንጣ ከሆነችው ኢራን ጋርም ድብቅ ግንኙነቷን እያጠናከረች ነው» እ.አ.አ በሰኔ 2017 ከአገሪቱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቋረጣቸው የሚታወስ ነው፡፡ ሊቢያ፣ የመን ማልዲቭስና ሌሎች ሀገራትም የነሳዑዲ አረቢያን ፈለግ ተከትለው ከኳታር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያቋረጡ ሀገራት መሆናቸው ይታወሳል፡፡
በዚህም ሀገራቱ ከኳታር ጋር የሚዋሰኑባቸውን የየብስና የምድር ወሰኖች ከመዝጋታቸውም በተጨማሪ የአየር ክልላቸውን ዝግ በማድረግ ከኳታር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ አቋርጠዋል፡፡ ኳታር በበኩሏ በነሳዑዲ አረቢያ የቀረቡባትን ክሶች በተደጋጋሚ አስተባብላለች፡፡ አገራቱ ግንኙነታቸውን ካቋረጡ ወዲህ ሁለቱን ወገኖች ለማደራደር የተደረጉት ጥረቶች እስካሁን ሳይሳኩ ቀርተዋል፡፡
ልዕለ ኃያላኗ አሜሪካም በቀጣናው ተጨማሪ የፀጥታ ስጋት እንዳትፈጠር ኳታርና ሌሎቹ የባህረ ሰላጤው አገራት የገቡበትን ፖለቲካዊ ውዝግብ እንዲፈቱ ቀደም ብላ ጥሪ አቅርባ ነበር፡፡ ለአብነት ያህል ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ነሐሴ ወር ኳታርና ሌሎቹ የባህረ ሰላጤው ሀገራትና የገቡበትን ፖለቲካዊ ውዝግብ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈቱት ከሳዑዲ አረቢያው ንጉሥ ሳልማን ቢን አብደል አዚዝ አል-ሳዑዲ ጋር እንደተወያዩ ይታወሳል፡፡ በውይይታቸውም፣ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የባህረ ሰላጤው አገራት ትብብርና አንድነት አስፈላጊ በመሆኑና ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሰኔ ወር ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተጉዘው ሽብርተኝነትን በጋራ ለመዋጋት ከሳዑዲ አረቢያ ጋር የተስማሙበትን ስምምነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ሀገራቱ የገቡበትን ውዝግብ በዲፕሎማሲ እንዲፈቱ ፕሬዚዳንቱ ለንጉሡ እንደነገሯቸው በወቅቱ ተገልፆ ነበር፡፡
በሌላ በኩል ፕሬዚዳንቱ በዚያው በሰኔ ወር ከኳታሩ ኢሚር ሸህ ታሚን ቢን ሐማድ አል-ታሃኒ ጋር በስልክ ባደረጉት ውይይት፣ አሜሪካ የባህረ ሰላጤው አገራት የገቡበትን ፖለቲካዊ ውዝግብ ለማብረድ ተሳትፎ ለማድረግ እንደምትሻና ለዚህም ዝግጁ መሆኗንና አስፈላጊ ከሆነም በዋይት ሃውስ ቤተ-መንግሥት ተገናኝተው ለመምከር መዘጋጀታ ቸውንም ገልፀውላቸው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
አሜሪካ የባህረ ሰላጤው አገራት ውዝግባቸውን እንዲፈቱ የፈለገችው ኳታር ከባህረ ሰላጤው ጎረቤቶቿ ከተገለለች ወዲህ ከኢራን ጋር የጀመረችው ጠንካራ ግንኙነት የትራምፕን አስተዳደር ስላሳሰበው እንደሆነ የሚገልፁ የፖለቲካ ተንታኞች አሉ፡፡
የቭላድሚር ፑቲኗ ሩስያ በበኩሏ ኩዌት የጀመረችውን ሁለቱን ወገኖች የማደራደር ጥረት እንደምትደግፍ አስታውቃ ነበር፡፡ ውዝግቡን ለመፍታት ብቸኛው አማራጭ ድርድርና ውይይት እንደሆነና አማራጮችን ለመፈለግ ዝግጁ እንደሆነችም ገልፃ ነበር፡፡
የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ኳታርና ማዕቀብ የጣሉባት አገራት የሚከተሉት የማኅበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መዋቅር ስር ለሰደደ ቁርሾና መቃቃር ዳርጓቸዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ኳታር ከአብዛኞቹ የአረብና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት በተለየ መልኩ የምታራምደው ላላ ያለ የፖለቲካ ምኅዳር ጎረቤቶቿ ጥርስ እንዲነክሱባት ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡፡

አንተነህ ቸሬ

Published in ዓለም አቀፍ

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከመ ሰንበቻው የሰጠውን መግለጫ ተንተርሰው አንዳንድ ፅንፈኛ ኃይሎች መግለጫውን ገና ከመስማታቸው የተለመደውንና ኅብረተሰቡን ያደናግርልኛል የሚሉትን «ኢትዮጵያ ፈርሳለች» ዲስኩር ሲያስደምጡን ሰንብተዋል። ይህ በእውነቱ እጅግ አስገራሚና አስቂኝ ጉዳይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። እነዚህ ኃይሎች ወትሮም ቢሆን «ወደቀ» የሚል ጉዳይ ሲሰሙ ተሰበረ የሚሉ ናቸው።
እርግጥ የ«ኢትዮጵያ ተበታተነች» ሟርት ዛሬ የተጀመረ አይደለም። እነዚህ ፅንፈኞች ከዛሬ 26 ዓመት በፊት ተመሳሳይ ነጠላ ዜማን በአንድ ዓይነት ቅላፄ ሲያቀነቅኑ የነበሩ ናቸው። ልዩነቱ ከዛሬ 26 ዓመት በፊትና ዛሬ መባሉ ነው። ግና ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ከብተና ያዳነ ድርጅት እንጂ ሀገርን ወደ ብተና የሚመራ ኃይል አይደለም።
እንኳንስ ዛሬ ያኔም ቢሆን ድርጅቱ ችግሮችን ከሕዝቡ ጋር በመሆን እንደ አመጣጣቸው የመፍታት ጥንካሬ ይዞ ያደገ ነው። የኢህአዴግ መስመር በደርግ ውድቀት ማግስት ‘ኢትዮጵያ ልትበታተን ነው’ በማለት ሲያሟርቱ የነበሩ ተንታኝ ተብዬዎች ጥንቆላ መና እንዲቀር ያደረገ የሰላም ጎዳና ነው። መስመሩ ሀገራችን ሰላም እንድትሆን ያደረገ ብቻ ሳይሆን፤ ከብተናም እንድንድን ያደረገን መሆኑን ማንም መዘንጋት የለበትም። ያም ሆኖ ግን መግለጫው ፅንፈኞች እንደሚሉት ዓይነት አይደለም።
እርግጥ መግለጫው በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች ሊኖሩ ቢችሉም፤ ኢህአዴግና መንግሥት ግን በመግለጫው ላይ ችግሩን ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም መያዛቸውን የሚያስረዳ እንጂ ስለ ሀገር ብተና የሚያወራ ነገር የለውም። ምንም እንኳን እያንዳንዱ ጉዳይ በመግለጫ ውስጥ ሊዘረዘር የሚችል ባይሆንም፤ ፅንፈኞቹ ስለ መግለጫው አንዳች እውቀት ሳይኖራቸው ተሽቀዳድመው «ሲሮጡ የታጠ ቁት…» ዓይነት በመሆን ‘በቃ! ሁሉም ነገር አበቃለት!’ የሚል የማደናገሪያ ስልት መያዛቸው መልሶ ራሳቸውን ግምት ላይ የሚጥላቸው ነው።
እንደ እውነቱ ከሆነ ፅንፈኞቹ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለ17 ቀናት ግምገማ ሲቀመጥ ምንም ዓይነት ፍንጭ ሊያገኙ ባለመቻላቸው ይይዙትና ይጨብጡት ነገር አጥተው እንደነበር ግልፅ ነው። በ«ይሆናል» መላ ምት ሲታመሱ እንደነበር ማንም አይዘነጋውም። ገሚሱ ፅንፈኛ ‘የእነ እገሌ ድርጅት አልተስማማም’ ሲል፤ ሌላው ደግሞ ‘እነ እገሌና እነ እገሌ ተጣሉ’ የሚል የመንደር አለሉባልታን በየማህበራዊ ሚዲያው ላይ ሲደሰኩሩ ነበር። መግለጫው እንደ ወጣም ‘በቃ አከተመለት’ የሚል ልቦለዳዊ ድርሰትን ደረሱ።
ከድርሰታቸው ውስጥ እጅግ ያሳቀኝ ጉዳይ ቢኖር ‘የሽግግር መንግሥት መስርተናል’ የሚሉና የሀገራችንን ሕዝብ የማይመጥኑ በውጭ የሚኖሩ አስቂኝ ፅንፈኞች ናቸው። በእነርሱ ቤት ውጭ ሆነው የሽግግር መንግሥት ለመመስረት ተፈራ ርመው ያለ አንዳች ሃፍረት ከራቫታቸውን አስረው በቦሌ በኩል ሲመጡ‘ጉሮ ወሸባዬ’ እያልን እንድንቀበላቸው እየነገሩን ነው።
እንግዲህ በወረቀት ላይ ፊርማ አራት ኪሎ ቤተመንግሥት ሊገባ መሆኑ ነው። ለእነርሱ የሕዝብ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነት፣ የሀገር ውስጥ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ምናቸውም አይደሉም። የቀን ቅዠታቸው ሥልጣንና ሥልጣን ብቻ ነው። መቼም ‘ጆሮ አይሰማው የለ’ ከማለት ውጪ ከቶ ምን ማለት ይቻል ይሆን?-ምንም። የእነዚህን «ላም አለኝ በሰማይ…» ባዮች የህልም እንጀራ እዚህ ላይ ልግታውና ወደ ኢህአዴግ መግለጫ ላምራ።…
ቀደም ሲል እንዳልኩት ኢህአዴግ በአመራሩ ውስጥ በነበረው ችግር ምክንያት በሀገራችን ውስጥ በጊዜያዊነት የተከሰተውን ግጭት በቁርጠኝነት ለመፍታት ግልፅ አቋም ወስዷል። ይህ አቋም የወሰደውም አመራሩ በችግሮቹ ላይ ተማምኖ የጋራ አንድነት ፈጥሮ እንደ ቀድሞው አንድ ዓይነት ስምምነት ላይ በመድረሱ ነው። ተበታትኖና ተለያይቶ አሊያም ፅንፈኞች እንደሚሉት ‘እገሌ ከእገሌ ጋር ተጣልቶ’ አይደለም።
ታዲያ ይህን እውነታ ከመግለጫው ላይ «የድርጅታችን ግምገማ በመላው የአገራችን ሕዝቦች ከባድ ተጋድሎ የተመዘገቡ ስኬቶችን ለመጠበቅና ለማስፋት እንዲሁም ከምንም ነገር በላይ በአመራር ድክመት የተፈጠሩትን አደጋዎችና ስጋቶች ለመቅረፍ በሚያስችል ስምምነትና መግባባት ተጠናቅቋል» በማለት ያሰፈረውን አቋም መግለፅ የተነሳሁበትን ነጥብ ይበልጥ የሚያደረጅልኝ ይመስለኛል።
የድርጅቱ መግለጫው በተፈጠው የአመራር ስህተት የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመካስ ቁርጠኛ መሆኑንም አስታውቋል። ይህ ማለት በድርጅቱ ፈጣን አመራር የመስጠት ችግር ምክንያት ሀገራችን ውስጥ የተፈጠሩ ችግሮች ይስተካከላሉ፣ ከእንግዲህም የሕዝብ ግጭት መነሻ የማይሆኑበት ደረጃ ለማድረስ በቁርጠኝነት እንሰራለን ማለት ይመስለኛል። ይህንን ሁኔታም የአራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት በመገናኛ ብዙኃን ሲገልጹ አድምጠናል።
እንደ እውነቱ ከሆነ ኢህአዴግ አንድን ነገር «እፈፅማለሁ» ካለ እንደተፈፀመ መቁጠር የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ምክንያቱም ከድርጅቱ ቀዳሚ ታሪክ እንደምንረዳው፤ ገዥው ፓርቲ አደርገዋለሁ ብሎ ያልፈፀመው ነገር አለመኖሩ ነው። ይህ ማንነቱም በሕዝቡ ውስጥ እንደ ፅንፈኞቹና እንደ አንዳንድ ሁሌም ከል ደመና ብቻ የሚታያቸው የሀገር ውስጥ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ምራጭ ሳይሆን፣ ተመራጭ ያደረገው ነው ብዬ አስባለሁ።
በእኔ እምነት ኢህአዴግ የማያደርገውን ነገር አደርጋለሁ ብሎ ቃል አይገባም። ይህን ማንነቱን ከዛሬ 16 ዓመት በፊት አሳይቶናል። በወቅቱ ለመታደስ ቃል በገባው መሠረት መታደስ ብቻ ሳይሆን ከተሃድሶው በኋላ በተከተላቸው ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ሀገራችንን የልማት ተምሳሌት ማድረግ ችሏል። የዓለም ሀገራት ዘንድ ተፈላጊ እንድትሆንም አድርጓታል።
ዛሬ የኢህአዴግን መስመር አፍሪካዊ ወንድሞ ቻችን እንደ «ሞዴል» እየተወሰደ ነው። ድርጅቱ ከትናንት ችግሮቹ እየተማረና ፈተናውንም በአጥጋቢ ውጤት እያለፈ የመጣ ሕዝባዊ ኃይል በመሆኑ፤ ነገም ዛሬ የገባውን ሕዝብን የመካስ ቃል እንደ ሚፈፅም በርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ምክንያቱም ድርጅቱ የሕዝብን የለውጥ ፍላጎት ሲመራ የመጣና ወደፊትም የሚመራ የሕዝብ አገልጋይ በመሆኑ ነው።
በመሆኑም ራስን አሂሶ የሕዝብን ችግር በቁርጠኝነት ለመፍታት ቃል በመግባትና በመግለ ጫውም ላይ «ከውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ አኳያ አሁን የተጀመረውን ግምገማ መሠረት በማድረግና የትራንስፎርሜሽን አጀንዳችንን በውጤት ለማስፈ ፀም እያንዳንዱ ብሔራዊ ድርጅት በከፍተኛ አመራር ደረጃ የሚታይበትን ድክመት በጥልቀት ገምግሞ በግልጽነትና በተጠያቂነት ላይ የተመሰረተ የማስተካከያና የእርምት ርምጃ እንዲወስድ ወስኗል» ብሎ ተገቢ መንገድን መከተል ለፅንፈኞቹ እንዴት «ኢትዮጵያ አበቃላት» የሚል የማደናገሪያ ሰበዝ ሊያስመዝዝ እንደቻለ የሚገባው ለእነርሱ ብቻ ይመስለኛል። ገና ለገና ምኑንም ሳያዩና ተሽቀዳድመው ተረት-ተረት ለማውራት መሞ ከራቸው እነዚህ ኃይሎች ምን ያህል እዚህ ሀገር ውስጥ ካለው የፖለቲካ ተጨባጭ ሁኔታ የራቁ መሆኑን አመላካች ነው። እናም ነገረ ሥራቸው «ሲሮጡ የታጠቁት…» ሆኖ፤ ለላኪዎቻ ቸው የሚሯሯጡት ፅንፈኞች በሚያራምዱት ባዶ ሃሳብ ሊያፍሩ የሚገባቸው ይመስለኛል። ህሊና ላለው ሰው ከዚህ በላይ ውርደት አይኖርም።
ያም ሆኖ እነርሱና አንዳንድ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች እንደሚመኙት የምትበታተን ሀገር የለችንም። ኢትዮጵያ ዛሬም ይሁን ነገ በሕዝቦች የመስዋዕትነት ድል ያገኘችውን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ በማጠናከር ዓለም አቀፋዊ ተሰሚነቷን እየጨመረች ነገ ይበልጥ ከፍ ያለ ቦታ ላይ መገኘቷ አይቀሬ ነው። የዚህ አባባል መሠረቱ ኢህአዴግና ሕዝቡ ያላቸው የማይላላ ግንኙነት ነው። እናም እውነታውን ፅንፈኞቹም ይሁኑ ላኪዎቻቸው ሁሌም ሊያውቁ የሚገባ ጉዳይ ነው።

 ቶሎሳ ኡርጌሳ

Published in አጀንዳ

ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ የመልክዓ ምድር አቀማመጥ፣ የአየር ንብረትና የሕይወታዊ ሀብት ስብጥር ጸጋ ካላቸው የዓለም አገሮች አንዷ ነች፡፡ ይህ በዕፅዋት፣ በእንስሳትና በጥቃቅን ሕዋሳት የሚካተተው ሕይወታዊ ሀብቷ ለሀገሪቱ የግብርና፣ የኢንዱስትሪና የጤና ዘርፎች እድገት እንዲሁም ለሌሎች ማኅበራዊና ልማት ነክ ተግባራት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡
የሕዝብ ቁጥር ከልማት ዕድገት ጋር ያለመጣጣም፣ የአየር ንብረት ለውጥ መከሰት፣ ይህንን ተከትሎም የድርቅና ምርታማነት መቀነስ እንዲሁም የሕይወታዊ ሀብት ጥበቃን ያላገናዘቡ የግብርናና የኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ መሆን፣ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ፋብሪካዎች የአካባቢንና የሕዝብን ጤና አደጋ ውስጥ መክተታቸው በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት አሳሳቢ አድርገውታል፡፡
መንግሥት ኢንዱስትሪዎች ከብክለት ነፃ በመሆን የምርት ሥርዓታቸውን የሚያከናውኑበት ቴክኖሎጂ ተግባራዊ እንዲሆን አስገዳጅ ሕግ ቢያወጣም በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች ከፋብሪካዎች የሚለቀቀው ዝቃጭ አካባቢን፣ ወንዞችንና ሐይቆችን እየበከለ መሆኑ በምሬት ይገለፃል፡፡
ከብክለት ነፃ የሆነ የኃይል ምንጭ በመገንባት ከድህነት ለመውጣት ከሚከናወኑ ተግባራቶች መካከል አንዱ_የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ነው። በተለይ የአገሪቱ _የኃይል አቅርቦት ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ በመሆኑ ትላልቅ የኃይል ማመንጫዎችን መገንባት _ካልተቻለ _ሊገኝ የሚፈለገው ዕድገት የሚታሰብ አይሆንም።
የኢትዮጵያውያን አንድነትና ትብብር _የተገለፀበት የህዳሴ ግድብ ትውልድ ተሻጋሪ የልማት ቱርፋት ሲሆን፤ ዜጎች አንድነታቸውን አጠናክረው _የውጭ ወራሪን በመመከት ጊዜ የማይሽረው ታሪክ እንደሰሩት ቀደምት ትውልዶች ሁሉ ታላቁን ግድብ በመገንባት ታሪክ እየሰሩ ይገኛሉ።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን እንደ አባቶቻቸው የሕይወት መስዋዕትነት መክፈል ሳይጠበቅባቸው ለልማት የሚውል ላባቸውን በማፍሰስ አገሪቱን የማሳደግ ታሪክ መስራት እየቻሉ ነው። ለዚህ ምስክሩም በአገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የሁሉንም ሕዝቦች ቀልብ መግዛትና ሁሉን አቀፍ ሕዝባዊ ንቅናቄ መፍጠር የቻለው የህዳሴ ግድብ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት_በበርካታ አካባቢዎች ኅብረተሰቡ ለአካባቢ ጥበቃ ሥራ እንዲነሳሳ ዕድል ተፈጥሯል። ኅብረተሰቡ የግድቡ ዕድሜ እንዲጨምር _የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን በተለይም በችግኝ ተከላና አፈር ጥበቃ ሥራዎች ላይ እየተረባረበ ይገኛል። ይህ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በገንዘብ ሊተመን የማይችል ነው። ይህም ለተያያዝነው አረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ሰፊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። የአገሪቱ ስነ ምህዳርም በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻል በማሳየት ላይ ነው።
ይሁን እንጂ በርካታ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ከመሆናቸው በፊት በአካባቢ ላይ ሊያደርሱ ስለሚችሉት ጉዳት አካባቢያዊ ተፅዕኖ ግምገማ አካሂደው ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ በጥናታቸው መሠረት ለአካባቢ የሚያደርጉትን ጥበቃ ቃል በገቡት መሠረት እየተወጡ አይደለም፡፡ በዚህ ሁኔታም በሐይቆችና በውኃ አካላት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች በርካታ ናቸው፡፡
በባለሙያዎች አገላለፅ ለሐይቆችና ለውኃ አካላት ጉዳት ዋናው መንስዔ በተራራማ አካባቢዎች የሚካሄዱ የእርሻ ሥራዎች ሲሆኑ፤ እንዲህ ያሉትን አካባቢዎች ለእርሻ ሥራ ማዋል ሐይቆች በደለልና በወራሪ አረሞች እንዲሞሉ ምክንያት ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያም በእነዚህና በሌሎች አካባቢያዊ ተፅዕኖዎች ምክንያት ሐሮማያና ጣና ሐይቅ የጉዳቱ መገለጫ ሆነዋል፡፡ እንደ ሻላና አብያታ ያሉ የስምጥ ሸለቆ ሐይቆችም የመድረቅ አደጋ እንደተጋረጠባቸው ይታወቃል፡፡
ባለፉት ዓመታት ከሀገሪቱ አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር አብላጫውን የሚወክለውን አርሶ አደር በተፋሰስ ልማቱ ዋነኛ ተዋናይና የሥራው ባለቤት እንዲሆን በማስቻል ሰፊ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ በተያዘው ዓመትም ከጥር አንድ ጀምሮ በርካታ አርሶ አደሮችን ያካተተ የተፋሰስ ልማት ሥራ ተጀምሯል፡፡ ከዚህ አንፃር የተገኘው ውጤት ቀላል የማይባልና ለበርካታ ሀገራትም በምርጥ ምሳሌነት ቢቀርብም ተከታታይ ሥራዎች ካልተከናወኑ ዘላቂ ውጤት ሊገኝ አይችልም፡፡
በደን ላይ ጭፍጨፋ ማካሄድ፣ ለአካባቢ ጥበቃ የሚያግዝ ጠንካራ ሕግ አለመኖር፣ ለአካባቢ ሥነ ምህዳር መጠበቅ የማይበጁና የሚያጎሳቁሉ ሕገወጥ ተግባራት መፈፀምና በአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ላይ ምክር የሚሰጡ አማካሪዎች ብቃት አጠያያቂ መሆን ለተጀመረው የአረንጓዴ ልማት እንቅፋት ስለሚሆን የሚታዩ ጉድለቶችን በፍጥነት በማረም ልማቱን ማስቀጠል በቸልታ ሊታለፍ አይገባም፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

አዲስ አበባ፦ የ2010 ዓ.ም የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ዋነኛ የትኩረት ማዕከሉ ጥራት ላይ የተመሰረተ ሥራ ማከናወን እንደሆነ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ብርሃኑ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ የዘንድሮውን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት በጥራት ለማከናወን የተደረገው ቅድመዝግጅትና ሰፊ ርብርብ ባለፉት ዓመታት ከተከናወኑ ተመሳሳይ ተግባራት የተለየ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ 

ቀደም ባሉት ዓመታት የተከናወኑት ሥራዎች ብዙ ውጤቶች የተገኙባቸው ቢሆኑም በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ሥራዎቹ ከተሰማራባቸው የሰው ኃይል አንፃር ሲታይ ጥራታቸው የተጓደሉባቸው እንደነበሩ ኃላፊው አስታውሰው፣ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው ወቅት የተሠሩ እርከኖች የመፈራረስና የመደፈን እንዲሁም የሚተከሉ ችግኞች በተፈለገው መጠን አለመጽደቅ ችግሮች እንደነበሩ ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ለዘንድሮው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ የተደረገው ቅድመዝግጅት ለችግሮቹ ዘላቂ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በተፋሰስ ልማት ሥራው ላይ ከ10 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደ ሚጠበቅና ለሥራውም በሁሉም ክልሎች የሚገኙ 6ሺ700 የሚሆኑ የተፋሰስ ልማት ቦታዎች መለየታቸውን የጠቆሙት አቶ ዓለማየሁ፣ ቀደም ባሉት ዓመታት ከተከናወኑት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች የተገኙ መልካም ተሞክሮችን በመቀመር ዘንድሮ ጥራቱ የተጠበቀ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ለማከናወን የሚያስችሉ የትኩረት አቅጣጫዎች እንደተቀመጡም አስረድተዋል፡፡
እስከአሁን ድረስ በዘመቻ መልክ ሲከናወን የቆየውን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ በቋሚነት የሚከናወን ተግባር በማድረግ የሥራውን ዘላቂነትና አስተማማኝነት ለማረጋገጥ እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የአገሪቱን ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ ተግባራት እንደሚጠበቁ አቶ ዓለማየሁ ጠቁመዋል፡፡

አንተነህ ቸሬ

Published in የሀገር ውስጥ

አዲስ አበባ፡- አገሪቱ ለዓለም ገበያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች (ከሆርቲካልቸር ዘርፍ) በዓመት 300 ሚሊዮን ዶላር እያገኘች መሆኑን የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራች ላኪዎች ማህበር ገለጸ፡፡ ማህበሩ በዘርፉ የተሰማሩ ከአንድ መቶ በላይ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ዓለም አቀፍ ‹‹ሆርቲፍሎራ 2018 ኤክስፖ›› በአዲስ አበባ እንደሚካሄድም አስታውቋል፡፡ 

በአዲስ አበባ ከተማ እ.አ.አ ከማርች 14 እስከ 16 ቀን 2018 የሚካሄደውን ሰባተኛው ዓለም አቀፍ ‹‹ሆርቲፍሎራ 2018 ኤክስፖ›› ኤግዚብሽን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራች ላኪዎች ማህበር ከትናንት በስትያ በሰጠው መግለጫ የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ዘውዴ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በሆርቲካልቸር ዘርፍ የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ሃይላንድ ስትሮበሪ ምርቶችን ለዓለም ገበያ እያቀረበች ሲሆን፤ ከዘርፉ በዓመት 300 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ታገኛለች፡፡
ሆርቲካልቸር ዘርፍ ለ200 ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንና በአሁኑ ወቅት አበባ በ1 ሺ 600 ሄክታር መሬት ላይ እየተመረተ እንደሚገኝ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ አገሪቱ በዘርፉ ካላት እምቅ አቅም አንጻር ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ማህበሩ የአገሪቱን አቅም ለማስተዋወቅ፣ አቅም ያላቸውን ኢንቨስተሮች ለመሳብ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ የመብራት ዋጋ አነስተኛ መሆን፣ በአነስተኛ ዋጋ የመሬት አቅርቦት መኖር፣ በተመጣጣኝ ክፍያ የሰው ኃይል መኖር በአገሪቱ ዘርፉን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታዎች መሆናቸውን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ፣ የመንግሥት አሠራር ውጣ ውረድ የበዛበት መሆን የዘርፉ ተግዳሮቶች ሲሆኑ፤ በቀላሉ ሊበላሹ የሚችሉ ምርቶች የሚላኩበት በመሆኑ አፋጣኝ ምላሽ ያስፈልጋል፤ የቢሮክራሲ መጓተቶችም መሻሻል አለባቸው፡፡ በተለይም ውድድሩ የተደራጀ የቢሮክራሲ ስርዓት ካላቸው አገራት ማለትም ኔዘርላንድ፣ ኮሎምቢያና ኢኳዶር ጋር በመሆኑ ዘርፉን ወደ ኋላ ሊጎትቱ የሚችሉ ችግሮች ሊፈቱ ይገባል፡፡ የዘርፉ ውጤታማነት በመሰረተ ልማት፣ በቢሮክራሲና በአጠቃላይ የሎጂስቲክ አገልግሎት ስለሚወሰን ሁሉንም ሴክተሮች በማቀናጀት መሥራት ያስፈልጋል፡፡
ዳይሬክተሩ አክለው፤ አገሪቱ በዘርፉ ያላትን አቅም ለማስተዋወቅ እ.አ.አ ከማርች 14 እስከ 16 ቀን 2018 ለሰባተኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ‹‹ሆርቲፍሎራ 2018 ኤክስፖ›› ኤግዚብሽን እንደሚካሄድና ከአውስትራሊያ፣ ከደቡብ ኮሪያ፣ ከቻይና፣ ከጃፓን፣ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ አገራት፣ ከመካከለኛ ምሥራቅ እንዲሁም ከአፍሪካ አገራት እስከ 120 የውጭና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል፡፡
«በኤግዚቢሽኑ አምራቾች፣ ዓለም አቀፍ ገዥ ኩባንያዎች፣ ኬሚካልና ማዳበሪያ አምራቾችና አቅራቢዎች፣ አማካሪዎች፣ ቴክኖሎጂ አቅራቢዎች፣ በአይ.ሲ.ቲ. የተሰማሩ ኩባንያዎች ይሳተፋሉ፡፡ ይህም አገሪቱ በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም ለማስተዋወቅና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ያግዛል፡፡›› ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በመንግሥት የተለዩ አዳዲስ ኢንቨስትመንት ቦታዎችን ለማስተዋወቅ ታሳቢ ያደረገም ሲሆን፤ አዳዲስ ለሚመጡ ኢንቨስተሮች በባህርዳር፣ በአላጌ፣ በአርባምንጭና በሃዋሳ ቦታ መዘጋጀቱንና የውጭና አገር ውስጥ ኢንቨስተሮች በዘርፉ ለመሰማራት የአዋጭነት ጥናት እያጠኑ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ በአገሪቱ ዓመቱን በሙሉ ማምረት የሚቻልበት አየር ንብረት፣ የከርሰና ገጸ-ምድር ያልተበከለ ንፁሕ ውሃ መኖር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከመቶ በላይ መዳረሻዎች ያሉት መሆኑና በአሁኑ ወቅት የባቡር መምጣት ለዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ዑመር እንድሪስ

Published in የሀገር ውስጥ

አዲስ አበባ፡- ስትራቴጅክ መጠባበቂያ ምግብ ክምችት ኤጀንሲ በስድስት ቅርንጫፎች ማስፋፊያና በሰባት ሳይቶች አዳዲስ የእህል ማከማቻ መጋዘኖችን ለመገንባት ከሁለት ዓመት በፊት ቢያቅድም እስከአሁን ወደ ሥራ አለመግባቱን አስታወቀ፡፡

የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ዓለምነው ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደገለጹት ኤጀንሲው ማስፋፊያና አዲስ ግንባታ እንደሚያከናውን ሰኔ ወር 2008ዓ.ም ላይ ከጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ጋር ባካሄደው ቃለ ምልልስ መግለጹ ቢታወቅም እስከአሁን የግንባታም ሆነ የማስፋፊያ ሥራዎች አላከናወነም፡፡
ኤጀንሲው ወደሥራ ያልገባባቸውን ምክንያ ቶች ኃላፊው እንዳስረዱት መንግሥት አስፈላጊውን በጀት ቢያሟላም ለግንባታ ላቀረበው የቦታ ጥያቄ ከአንዳንድ ክልሎች ምላሽ አለማግኘቱ ፣ ኤጀንሲው ውስጥ የተጠናከረ የቴክኒክ ምህንድስና ክፍል አለመኖር፣ ሥራዎቹ ለውጭ ድርጅት በጊዜያዊ ውል መሰጠታቸውና ኃላፊነቱን የወሰዱት አካላትም በባለቤትነት ባለመሠራታቸው ዕቅዱን በወቅቱ ማሳካት አልተቻለም፡፡
በአሁኑ ጊዜ ግን በፍኖተ-ሰላም፣ ጅግጅጋና ሆሳዕና ከተሞች ባገኘው ቦታ ላይ በ3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ወጪ አዳዲስ ግንባታዎችን ለማከናወን ተቋራጮችን ለመለየት በጨረታ ላይ የሚገኝ መሆኑንና ግንባታውም በበጀት ዓመቱ እንደሚጀመር አመልክተዋል፡፡ ነቀምት፣ ባሌ ሮቤና ነገሌቦረና ትልቅ አቅም ያላቸው አዲስ ሳይቶች ለመገንባት የተያዘው ዕቅድ ግን በከተሞች ካለው የቦታ አቅርቦት ችግርና ክልሉ በተለያዩ ሥራዎች ከመጠመዱ ጋር ተያይዞ የቦታ ፈቃድ አለማግኘቱንና በዚህ ዓመት የግንባታ ሥራ እንደማይጀመር አስታውቀዋል፡፡ ነባር መጋዘኖች የአንድ ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ የእህል ዕርዳታን ለማሰራጨት ሲባል የተገነቡ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ሰፊ ክፍተቶች እንዳሉባቸውም ገልጸዋል፡፡
ኤጀንሲው ባለፈው ለዝግጅት ክፍሉ በሰጠው መረጃ፤ በኮምቦልቻ 25 ሺ ሜትሪክ ቶን የመያዝ አቅም ያላቸው አምስት ተጨማሪ ማስፋፊያ መጋዘኖች፣ በመቀሌና ወላይታ ሶዶ 20 ሺ ሜትሪክ ቶን የሚይዙ አራት፣በወረታ 80 ሺ 320 ሜትሪክ ቶን የመያዝ አቅም ያላቸው11፣ በአዳማ 100 ሺ ሜትሪክ ቶን የሚይዙ፣ በሻሸመኔ 80 ሺ ሜትሪክ ቶን የሚይዙ ስምንት ማስፋፊያ መጋዘኖች፤ባሌ ሮቤ 185 ሺ 314 ሜትሪክ ቶን የመያዝ አቅም ያላቸው 19፣ ነገሌቦረና 25 ሺ 554 ሜትሪክ ቶን መያዝ የሚችሉ አራት፣ ነቀምት 202 ሺ 350 ሜትሪክ ቶን የሚይዙ 21፣ ቀብሪደሃር 25 ሺ 554 ሜትሪክ ቶን የሚይዙ አራት፣ ሆሳዕና 187 ሺ 952 ሜትሪክ ቶን የሚይዙ 19 መጋዘኖች ፣ ፍኖተሰላም 185 ሺ 314 ሜትሪክ ቶን የመያዝ አቅም ያላቸው 19 አዳዲስ መጋዘኖች እንደሚገነቡና ለግንባታው የቦታ መረጣና የግንባታ ዲዛይን ሥራዎች መጠናቀቃቸውን መግለጹ ይታወሳል፡፡
ኤጀንሲው የሚያስገነባቸው መጋዘኖች የእህል ክምችት አቅሙን ከ673 ሺ ሜትሪክ ቶን ወደ 1ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ለማሳደግ የነደፈውን ዕቅድ ለማሳካት የሚያግዘው እንደነበርም ገልጿል፡፡

ዑመር እንድሪስ

Published in የሀገር ውስጥ

ኢትዮጵያ ለጥጥ ልማት የሚውል ሰፋፊ እና ምቹ የሆነ መሬት አላት፡፡ የሚገኘው ምርትም የሀገር ውስጥ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎችን የግብአት ፍላጎት ማሟላት ያስችላል፡፡ በመሆኑም ለጥጥ ልማት የሚውለው መሬት ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ሲነፃፀር የተሻለ በሚባል ደረጃ ላይ እንድትገኝ አድርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት የጥጥ ልማቱ በስድት ክልሎች እየተከናወነ ሲሆን፤ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አርሶ አደሮችና ባለሀብቶች ተሳታፊ ናቸው፡፡
ዘርፉ ከምርት ጀምሮ በጨርቃጨርቅ ፋብሪካ የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ከ150ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ በሀገሪቷ በመገንባት ላይ ያሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ 60 በመቶ የሚሆነው ግብአታቸው ጥጥ በመሆኑ ዕድሉ ከዚህ በላይ የሰፋ ይሆናል፡፡ የጥጥ ልማቱና ኢንዱስትሪው ተመጋጋቢ ሆነው እንዲዘልቁ በጥጥ ልማትና መዳመጥ ያለው ማነቆ ከወዲሁ ካልተፈታ በኢንዱስትሪ መር ሽግግሩ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳይኖረው ስጋት አሳድሯል፡፡ በ2006/2007 ዓ.ም የምርት ዘመን በሀገሪቱ የጥጥ ምርት ሽፋን 98 ሺ ሄክታር ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ ወደ 60 ሄክታር ወርዷል፡፡ በምርት ዘመኑ የተዳመጠ ጥጥ ከነበረበት 68ሺ ቶን ወደ 42 ሺ በማሽቆልቆሉ ነው ስጋቱን የፈጠረው፡፡
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አንድ ሺ 295 ሄክታር የጥጥ ማልሚያ መሬት ያላቸው ኢንጂነር ጌታሁን ሁሴን እንደነገሩን በአሁኑ ጊዜ በጥጥ ልማት መሸፈን የቻሉት ስድስት መቶውን ብቻ ነው፡፡ እርሳቸው እንዳሉት የተሻሻለ ምርጥ ዘር፣ መሬቱን መልሶ ለማልማት በቂ የሆነ የማዳበ ሪያና የፀረተባይ መድሃኒት አቅርቦት አለመኖር፣በአገልግሎት ላይ ያሉት የጥጥ መዳመጫዎች አለመ ዘመን፣ የፋይናንስና የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ድጋፍ አለማግኘትና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች የዘርፉ ማነቆዎች በመሆናቸው ያላቸውን መሬት ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም አልቻሉም፡፡
የጋምቤላ አግሮ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተወልደ ገብረግዚአብሔር በዘርፉ ያለውን ማነቆ በምሬት ይገልጻሉ፡፡ በተለይ በዘር ወቅት የፀረተባይ መድኃኒት አቅርቦት አለመኖር ፈታኝ ሆኖባቸዋል፡፡ መድኃኒቱ ቢገኝም ጥራቱ የተጓደለና ጥቅም ላይ የማይውል ይሆናል፡፡የተሻሻለና በቂ ዘር፣የመድኃኒትና አስፈላጊ ግብአቶች እንዲሁም የፋይናንስ ድጋፍ በሌለበት ስለምርት ማሳደግ ማሰብ እንደሚያዳግት ይገልጻሉ፡፡ የጥጥ ልማቱ ከመንግሥት ዘርፈብዙ ድጋፎችን እንደሚፈልግም ተናግረዋል፡፡
የጥጥ አምራቾች ማህበር የዘላቂነት መርህ አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ ወልዴ እንደተናገሩት ምርታማ ነቱ ላይ ትኩረት ባለመሰጠቱ ዕድገቱ አዝጋሚ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ልማቱ በመከናወን ላይ ያለው ከ25 ዓመታት በፊት በነበረ የጥጥ ዝርያ ነው፡፡ ማነቆዎችን ለይቶ በወቅቱ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አለማስቀመ ጥና የመፍትሄ አቅጣጫዎችም አለመተግበ ራቸው ችግሩን አባብሶታል፡፡
ምርቶቻቸውን የሚቀበሉ ፋብሪካዎችም ችግሮ ቹን ይጋራሉ፡፡ የአልመዳ ጨርቃጨርቅ ፋበሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተክለማርያም ተስፉ ፋብሪካቸው በጥራት መጓደልና በቂ አቅርቦት ባለማግኘት የምርት መስተጓጎል እንዳስከተለባቸውና በወጪ ንግዳቸው ላይም ተፅእኖ እንዳስከተለና የገበያ ዋጋ በአጭር ጊዜ ውስጥ መለዋወጥም ፈተና እንደሆነባቸው ፣ አምራቹና አገልግሎት ፈላጊው ተቀራርበው በውይይት ችግሮቻቸውን ለመፍታት ያለው ባህል ደካማ መሆን ለዘርፉ ማነቆ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡
ችግሩ በዘርፉ ላይ የሚገኙትን በልማቱ ላይ እንዳይቆዩ እና ተስፋም እንዲቆርጡ እያደረጋቸው ቢሆንም የኢትዮጵያ ጥጥ አምራቾች ማህበር ሰብሳቢ ሼህ የሱፍ ኡመር በማህበሩ በኩል የሚፈታውን መፍትሄ በመስጠት፣ ከአቅሙ በላይ የሆነውን ደግሞ ከመንግሥት ጋር በመሆን እየተሠራ እንደሚገኝና ባለፈው በጀት ዓመትም በስፋት በመሠራቱ ተስፋ ማሰቆረጥ ደረጃ ላይ የደረሰ ነገር አለመኖሩን አመልክ ተዋል፡፡ የተነሱት የዘርፉ ማነቆዎች አፋጣኝ መፍትሄ እንደሚያስፈልጋቸውና አቀናጅቶ መሥራት ላይ ያለውን ድክመት መፍታት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
በቅድመ እርሻና ከእርሻ በኋላ በጥጥ ልማቱ ቦታ በመገኘት በሙያና በአቅም ግንባታ ድጋፍ በመስ ጠት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢኒስቲትዩት ዘርፉ የሚመራበት ስትራተጂ አለመኖር ለችግሮቹ መባባስ ምክንያት እንደሆነ ካለፉ ተሞክሮዎች ለይቶ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ለመስጠት የ15 ዓመት የጥጥ ልማት ስትራቴጂ አስጠንቷል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ በአጭር፣በመካከለኛና በረጅም ጊዜ የሚፈቱ 12ያህል የዘርፉን ማነቆዎች መለየታቸውን ገልጸዋል፡፡ በሥራ ዘርፉ ላይ የሚገኙት በሙሉ አቅማቸው በማምረት እያደገ ያለውን የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ እንዲመ ግቡ ቅድመ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውንም ተናግረ ዋል፡፡
ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም ዘርፉን በቅንጅት ለመደገፍ የተደረገው ጥረት አናሳ እንደነበር በግምገማው መለየቱን በሚኒስቴሩ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ጥናት ክትትል ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ ዘሪሁን አበበ ገልጸው፤ ከውጭ ምንዛሬ፣ ከፕሮጀክት ፋይናንስ ድጋፍና ለአደጋ ጊዜ የኢንሹ ራንስ ሽፋን ካለመኖር ጋር ተያይዞ የሚቀርበውን ቅሬታ ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሚኒስቴሩ በውይይት ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ዜና ትንታኔ
ለምለም ምንግሥቱ

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።