Items filtered by date: Saturday, 13 January 2018

የሠራተኛው ስፖርት ለአገራችን ስፖርት መሰረት ነበር። በሠራተኛው መካከል የሚካሄደው ውድድር አንጋፋ ከመሆኑ ባሻገር ቀደም ባሉት ዓመታት አገራችን በተለያዩ ስፖርቶች ለምታስመዘግባቸው ስኬቶች ትልቁን ድርሻ ይወስድ እንደነበር ከታሪክ ለመረዳት ይቻላል። በተለይም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪካዊ ተጫዋቾች ከሆኑት መንግሥቱ ወርቁና ኢታሎ ቫሳሎ አንስቶ በርካታ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተጫዋቾች ከሠራተኛው ስፖርት እንደተገኙ ታሪካቸው ይመሰክራል።
አንጋፋው ጋዜጠኛና የኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ ነጋሪ ገነነ መኩሪያ(ሊብሮ) ሐምሌ 2009 ዓ.ም በታተመው የሠራተኛው ስፖርት መፅሔት ላይ ባደረገው ቃለ መጠይቅ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ አቅም የነበረው ሠራተኛው እንደሆነ ገልጿል። በተለይም በሦስተኛው አፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ አስተናግዳ ባነሳችው ብቸኛ ዋንጫ ከቡድኑ ስብስብ ሰማንያ በመቶው ሠራተኛው እንደነበር ይናገራል። ብሔራዊ ቡድኑ ዋንጫውን ሲያነሳ ግቦችን ያስቆጠሩት ተጫዋቾችም ከሠራተኛው የተገኙ ናቸው። በዚያን ጊዜ የነበሩት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ግማሽ ያህሉ ሠራተኛ ነበሩ። በወቅቱ ሜዳ ገብቶ ለመመልከት ለተማሪ ሃምሳ ሳንቲም ለሠራተኛ ደግሞ አንድ ብር ነበር። በብዛት ጨዋታዎችን በዚህ መልኩ ይከታተል የነበረውም ሠራተኛው ነበር። ይህም አቅም ስላለው ብቻም ሳይሆን ስፖርትን ስለሚወድ ጭምር ነበር። በአስራ ሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ሊቢያ ሲያቀናም ከሠራተኛው የተገኙ ተጫዋቾች ዘጠና በመቶ ያህል እንደነበሩ ገነነ ያስታውሳል።
በክለቦች ተሳትፎና እንቅስቃሴም ሠራተኛው የነበረው ሚና ጉልህ ነበር። በአፍሪካ ክለቦች ቻምፒዮና እንዲሁም በክለብ በከፍተኛ ደረጃ የሚሳተፈው የሠራተኛው ቡድን ነው። 1957 ዓ.ም ላይ ጥጥ ማህበር የመጀመሪያውን የክለብ ተሳትፎ በአፍሪካ ደረጃ በማድረግ እስከ ግማሽ ፍፃሜ ተጉዞ ነበር። ሌላው ይቅርና አሁን የአስራ ሁለት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን በመሰብሰብ ኃያል የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ዘጠና በመቶ የሚሆኑት ተጫዋቾቹ በተለያዩ ፋብሪካዎች ተቀጥረው የሚሠሩ እንደነበሩ ገነነ ይናገራል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ፈርሶ በ1977 ዓ.ም ላይ ወደ ሊጉ ተመልሶ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ቻምፒዮን ሲሆን፤ ትልቅ ድርሻ የነበራቸው ከሠራተኛው የተገኙ ተጫዋቾች ነበሩ።
የሠራተኛው ስፖርት ከእግር ኳስ በተጨማሪ በሌሎች የስፖርት ዓይነቶችም ለአገራችን ያበረከተው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በእግር ኳስ የሚሳተፍ ቡድን የአትሌቲክስ ቡድን የመያዝ ግዴታ ብቻ የነበረው ቢሆንም በወቅቱ እስከ አምስት ስፖርቶች ድረስ በመያዝ የሚሳተፉ ተቋማት እንደነበሩ ይነገራል። በርካታ ተቋማት በአትሌቲክስ፤ በቦክስ፤ በቅርጫት ኳስና በሌሎች ስፖርቶች የሚሳተፉ ስፖርተኞችን ይዘው በመንቀሳቀስ ሠራተኛው በስፖርት የነበረው ተሳትፎ ሰፊ ነበር። ለምሳሌ አውራ ጎዳናና ቡና በስፖርት እንዲሳተፉ ስፖርተኞችን ሠራተኛ አድርገው በመቅጠር ይንቀሳቀሱ እንደነበር ገነነ ያስታውሳል። ይህ ዓይነት ሁኔታ ሲፈጠርም የስፖርት ፉክክሩና የእኔነት ስሜቱ ከፍ ወዳለ ደረጃ አድርሶትም ነበር።
ከዚህ በተጨማሪ ሠራተኛው በስፖርት ያለው ተሳትፎ በእግር ኳስ ብቻ እንዳልነበረ በርካታ መረጃዎችን ከታሪክ ማጣቀስ ይቻላል። በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ በዳኞች፤ በተጫዋቾች እንዲሁም በተመልካቾች ሰፊ ድርሻ የነበረው ሠራተኛው ነበር። ከዚህ በዘለለ እስከ ትልቅ አመራርነትም በተለያዩ ፌዴሬሽኖች ሠራተኛው ትልቅ አቅም እንደነበረው መገንዘብ ይቻላል።
ይህ በአገራችን ብዙ ታሪክ ያለው የስፖርት መድረክ አሁን ላይ ቀደም ሲል በነበረበት የውጤታማነት ደረጃ ላይ ይገኛል ለማለት አይቻልም። በተለይም አገርን በትልቅ ደረጃ መወከል የቻሉ (ኢሊት) ስፖርተኞችን በማፍራት ረገድ በተለያዩ ምክንያቶች ክፍተቶች እንዳሉ መረዳት ይቻላል። በአንፃሩ የሠራተኛው ስፖርት ከቀድሞው በተሻለ መልኩ የተለወጡ በርካታ ነገሮች እንዳሉትም መመልከት ይቻላል።
በኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) አዘጋጅነት የሚካሄደው ዓመታዊ የስፖርት ውድድር ሦስት ዓይነት ገፅታን የተላበሰ ከፉክክርም በላይ በርካታ ዓላማዎችን የሰነቀ የስፖርት መድረክ ነው። ረጅም ወራትን ሠራተኛው በስፖርት አማካኝነት አብሮነቱን የሚያጠናክርበትና ልምድ የሚለዋወጥበት የበጋ ወራት የስፖርት ውድድር የበርካታ ድርጅትና ተቋማት ሠራተኞችን ማዕከል ያደረገ የውድድር መድረክ ሲሆን፤ የሠራተኛውን ዓመታዊ በዓል ታኮ የሚካሄደው የሜይ ዴይ ውድድር ሌላኛው አካል ነው። ክረምት ወራት ላይ በውቡ የወንጂ ሁለገብ ስቴድየም የሚካሄደው አገር አቀፍ የሠራተኞች ውድድርም በድምቀቱና አገር አቀፍ ሠራተኞችን በአንድ ላይ ለሁለት ሳምንታት በትንሿ ከተማ ይዞ የሚከርም ነው።
ሦስቱም የውድድር ገፅታዎች ሠራተኛውን ከማቀራረብና ልምዱን እንዲለዋወጥ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር በሠራተኛው መካከል ቤተሰባዊ ስሜት እንዲጎለብት ሚናቸው ቀላል እንዳልሆነ የኢሠማኮ የስፖርት ክፍል ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ካሳ ይናገራሉ። በእነዚህ ሦስት የውድድር መድረኮች ከተሳትፎ አኳያ በርካታ የሠራተኛ ማህበራት በአስር የስፖርት ዓይነቶች ይሳተፋሉ። ከጊዜ ወደ ጊዜም የተሳታፊ ማህበራት ቁጥር እየተበራከተ ተደራሽነቱም አገር አቀፍ ገፅታን እየያዘ ይገኛል። በተለይም የሴቶችን ተሳትፎ ከማጠናከር አኳያ ተጨባጭ ለውጦች እየታዩ እንደሚገኙ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተካሄዱ በሚገኙ ውድድሮች መታዘብ ይቻላል። ሠራተኛው በስፋት ከስፖርቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ተቋዳሽ እንዲሆን በማስቻል ረገድ ሊጠቀሱ የሚችሉ ለውጦች ታይተዋል። ይሁን እንጂ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ አገርን ሊያስጠሩ የሚችሉ ኢሊት ስፖርተኞችን በብዛት እንደ ቀድሞው ዘመን የማፍራቱ ጉዳይ ብዙ ርቀት መጓዝ አልቻለም።
የሠራተኛው ስፖርት ወርቃማ ዘመን በ1970ዎቹ የነበረው ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም እንዲሁም በፕሮፌሽናል ደረጃ በርካታ የውድድር አማራጮች ለሠራተኛው ስፖርት ሰፊና ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዲሆን ማስቻሉ ይታመናል። ከዚህ በዘለለ በርካታ የሠራተኞች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መኖራቸው ለስፖርቱ ዕድገት ጉልህ ሚና እንደነበረው አቶ ዮሴፍ ይናገራሉ። አሁን ላይ በሠራተኛው መካከል የሚካሄዱት ውድድሮች ሠራተኛው ቤተሰባዊ ትስስር እንዲኖረው፤ በስፖርት ጤንነቱን የጠበቀ አምራች እንዲሆንና የኢንዱስትሪውን ሰላም ለመጠበቅ ትኩረት የሚሰጥ ዓይነት ገጽታ ያለው ነው። በዚህ መንገድም ከአገራችን ስፖርት ጎን ለጎን የበኩሉን አስተዋጽኦ የማበርከት ዓላማን የሰነቀ ነው።
የማዘውተሪያ ስፍራ አሁን ላይ የሠራተኛው ስፖርት ትልቁ ፈተና ሆኖ ብናገኘውም ውድድሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከሩ ፉክክሮችም የተሻሉ እየሆኑ መምጣታቸውን የስፖርት ክፍል ኃላፊው ይናገራሉ። የውድድር መድረኩ እያደገ መጥቶም ፌስቲቫል ወደ መሆን ተቃርቧል። ነገር ግን በትልቅ ደረጃ ጎልተው የሚወጡ ስፖርተኞችን ለማፍራት የራሱ የሆነ ችግር እንዳለበት ያብራራሉ።
የሠራተኛው ስፖርት ከዩኒቨርሲቲና ሌሎች ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው በሥራ ላይ የሚገኙ በርካታ ወጣቶች የሚሳተፉበት እንደመሆኑ መጠን በተለያዩ ስፖርቶች ትልቅ ተሰጥኦ ያላቸው ስፖርተኞች አይጠፉበትም። እነዚህ ወጣት ሠራተኞች ከሠራተኛው ስፖርት ባለፈ በትልልቅ የአገሪቱ ሊጎችና ውድድሮች የመሳተፍ ፍላጎት አላቸው። ይሁን እንጂ እነዚህን ተጫዋቾች በትልቅ ደረጃ የሚገኙ ክለቦችና አሰልጣኞች የመመልከት ዝንባሌያቸው ዝቅተኛ መሆኑን አቶ ዮሴፍ ያስረዳሉ። እነዚህ ስፖርተኞች በትልቅ ደረጃ ሳይጫወቱ ተደብቀው ይቀራሉ።
የሠራተኛው ስፖርት ብዙ ትኩረት በማይሰጣቸው ዘመናዊና የባህል ስፖርቶች ላይ እያከናወነ የሚገኘው ተግባርም በጥሩ ጎኑ መነሳት ያለበት ነው። ለአብነት ያህል ብዙ ውድድር ሲደረግባቸው የማይታዩት ገበጣ፤ ዳርት፤ ከረንቦላና ገመድ ጉተታን የመሳሰሉ ውድድሮች በሠራተኛው ስፖርት ቦታ ተሰጥቷቸው ጥሩ ፉክክር ይደረግባቸዋል። የተሻለ ፉክክር በሚደረግበት በተወዳጁ እግር ኳስም ቢሆን በሁለት ዲቪዚዮን ተከፍሎ የሚፎካከሩ ሠላሳ ያህል ማህበራት ይገኛሉ። በእነዚህ ውድድሮች አገርን ወክለው እንደ ቀድሞው በትልቅ ደረጃ ሊጫወቱ የሚችሉ ስፖርተኞች ቢኖሩም ከአሰልጣኞችና ክለቦች በተጨማሪ መገናኛ ብዙሃን የሚሰጧቸው ትኩረት አነስተኛ መሆኑ አቶ ዮሴፍ ገልጸዋል።
ውድድሩ የሠራተኞች እንደመሆኑ ሠራተኛው ብቻ መሳተፍ አለበት የሚሉ በርካታ አስተያየቶች ከስፖርት ቤተሰቡ ይሰማል። ገነነ መኩሪያም በመፅሔቱ ላይ ባደረገው ቃለ መጠይቅ በዚህ እንደሚስማማ አስቀምጧል። «በፋብሪካ ኢንዱስትሪ ውድድር ጊዜ ሠራተኛ ካልሆንክ በፍፁም አትጫወትም፤ በ1972 ዓ.ም ቡናና አልሙኒየም ቡድን ሲጫወቱ ቡና ሁለት ዕድል ይዞ ገብቶ ተሸንፎ ዋንጫውን አጣ፤ ቡናዎችም የአልሙኒየም ቡድን ሠራተኛ ያልሆነ ተጫዋች አጫውተዋል በማለት ከሰሱ፤ ታደሰ ሊዬ የሚባል ተጫዋች ነው ብለው አሰልፈውት ስለነበር አስተማሪ መሆኑ በተረጋገጠ ጊዜ ቡና ዋንጫ አግኝቷል» የሚለው ገነነ በዚያን ዘመን በሠራተኛው ስፖርት እንዲጫወት የሚፈቀድለት ሠራተኛ ብቻ እንደነበር ይናገራል። ለዚህም ስፖርተኞቹ የሥራ ደመወዝ ፔሮል ላይ ፈርመው የሚወስዱ መሆናቸውን በማሳያነት ያወሳል።
የሠራተኛ ስፖርት ውስጥ ቀድሞ ለመሳተፍ የሠራተኛ ማህበር መዋጮ የሚከፍሉ እንዲሁም በሠራተኛ መተዳደሪያ ደንብ ውስጥ የሚታቀፉ ናቸው። በ1975 ዓ. ም ስፖርቱ እንደ አዲስ ሲደራጅ እንኳን ከአንደኛው ዲቪዚዮን ከአስሩ ሰባቱ ሠራተኛ ቀጥረው የሚወዳደሩ ቡድኖች እንደነበሩ ገነነ ያስታውሳል። አብዛኛው ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ዲቪዚዮን ድረስ በርካታ ቁጥር የያዙትም ሠራተኞች ነበሩ። አሁን ግን ሠራተኞች እንዳልሆኑ ገነነ ይናገራል። በእርግጥም አሁን ላይ በተለይም በእግር ኳስ በሚደረገው ጠንካራ ፉክክር ከሠራተኛው ውጪ በከፍተኛና ብሔራዊ ሊግ ደረጃ ሲጫወቱ የምንመለከታቸው አንዳንድ ተጫዋቾችን ማየት የተለመደ ነው። የስፖርት ክፍል ኃላፊው አቶ ዮሴፍ እያንዳንዱ ማህበር አንድና ሁለት ተጫዋች ከሠራተኛ ውጪ አሰልፎ እንዲያጫውት እንደሚፈቀድለት ይናገራሉ። ይህም ፉክክሩን የተሻለ ለማድረግና የውድድሩን ደረጃ መጨመር ታስቦ እንደሆነ ያብራራሉ። ከሠራተኛው ውጪ እንዲጫወቱ የሚፈቀድላቸው በየቡድኑ አንድ ወይንም ሁለት ተጫዋቾችም በሌሎች ውድድሮች አቅምና ብቃት እያላቸው ዕድል ያላገኙ ናቸው። «ይህም የቡድኖችን ክፍተት ለመሙላትና ዕድል ያላገኙት ዕድል እንዲያገኙ ከማድረግ ባሻገር የሠራተኛው ስፖርት የተሻለ ልምድ እንዲኖረው ያደርጋል» ይላሉ አቶ ዮሴፍ።
እንደ ገነነ ገለጻ፤ ሠራተኛው በአሁኑ ጊዜ በኮሚቴ አመራርነት፤ በተጫዋችነትና ተወዳዳሪ ክለብ ከመመስረት አንፃር ስፍራውን ለቋል። ስለዚህ ይህን ለማሻሻል የተለየ ዘዴ መፈጠር አለበት። ይሄውም ትናንት የተካሄደበትን መንገድ መልሶ ማጤንና እሱን ባካተተ መልኩ ወደፊት አቅጣጫ መቀየስ ይገባል። ቀድሞ ሠራተኛው በቁጥር አነስተኛ በነበረበት ወቅት ጠንካራ ተወዳዳሪ የነበሩት ቡድኖች በመብራት ኃይልና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚወከሉት በሠራተኞች ነበር። አሁን ግን በሠራተኛው ስፖርት ባይሆንም በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከውጭ የተገዙ በከፍተኛ ገንዘብ ቢመጡም የሚፈለገውን ያህል ውጤት ሳያመጡ እንደ ንግድ ባንክ ዓይነቶቹ ሲወርዱ መብራት ኃይልም ቢሆን ከዓመት ዓመት ላለመውረድ ሲታገል ይታያል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ስፖርት ህግ ማዕቀፎችና አመራሮች ለሠራተኞች ስፖርታዊ ተሳትፎ ምቹ መሆናቸውንና አለመሆናቸውን በአሁኑ ጊዜ በባለሙያ ተጠንቶ በአግባቡ የሚታወቅበት ሁኔታ የሠራተኛ ወገን መሪዎች ሊያስቡበት ይገባል። እርግጥ ነው የሠራተኛው ስፖርት ወደ ፌስቲቫል ለማደግ ብዙ ርቀት ተጉዟል። አንድ ነገር ብቻ ግን ያሰጋዋል። ይህም የደጋፊ ወይም ተመልካች ቁጥር ከስፖርቱ እድገት እኩል አለማደጉ ነው። የኢሠማኮ የማህበራዊ ጉዳዮች ኃላፊና የስፖርት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ፍሰሃፂዮን ቢያድግልኝ ይህን ስጋት እንደሚጋሩት ከዚህ ቀደም ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ገልጸዋል። ነገር ግን እያንዳንዱ ተሳታፊ ማህበር ደጋፊውን ይዞ በመምጣት የውድድሩ ድምቀት እንዲሆን ኢሠማኮ ጥረቱን እንደሚቀጥል እምነታቸው ነው። የሠራተኛውን ስፖርት ወደ ታላቅ አገራዊ የስፖርት ፌስቲቫል ለማሳደግ ኢሠማኮ ባለፉት ዓመታት ያደረገው ጥረት ተጨባጭ ለውጥ እንዳመጣና የተሳታፊ ማህበራት ቁጥርን ማሳደግ ዋነኛው ተግባሩ እንደመሆኑ ወደ ፊትም ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል። በተለይም ኢትዮጵያ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ እየተሸጋገረች ባለችበት በዚህ ወቅት በርካታ ሠራተኞች ወደ ኢንዱስትሪ መምጣታቸው የግድ ነው። ኢሠማኮ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ ሠራተኛውን ወደ ስፖርቱ በማምጣት የጀመረውን ጥረት እንደሚቀጥል ይጠበቃል። የውድድሮችን ጥራትና ይዘት በማጠናከርም ሠራተኞች ጤንነታቸው የተጠበቀ አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ከማስቻልና እርስበርስ አንድነታቸውንና ህብረታቸውን ከማጠናከር በተጨማሪ ለአገራችን ስፖርት እድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥረቶች መቀጠልም ይኖርባቸዋል።
ተደጋግሞ እንደሚነሳው በኢሠማኮ የሚመራውን የሠራተኛው ስፖርት በዋናነት የገንዘብ እጥረት እየተፈታተነው ቢሆንም አቅም በፈቀደ መጠን ስፖርቱን ደማቅና ተወዳጅ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት አዳዲስ ማህበራትን ከያሉበት የመጥራት ብቃቱ ፣ የስፖንሰርሺፕና ማስታወቂያ ዋጋ እየጨመረ እንደሚሄድ ካለፉት ዓመታት ልምድ ተስፋ ሰጪ ፍንጭ ታይቷል።
የኢሠማኮ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎም የበጋ ወራት ውድድሩ ሲጀመር ባደረጉት ንግግር ይህንን በማረጋገጥ፤ በቀጣይ የሠራተኛውን ስፖርት በፕሮፌሽናል ደረጃ ከሚካሄዱ ውድድሮች ባልተናነሰ ድምቀትና ጤናማ የፉክክር መንፈስ ለማስቀጠል ጥረት እንደሚደረግ መናገራቸው ይታወሳል።
የሠራተኛው ቁጥር በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በጨመረበት ሁኔታ የሠራተኛው የስፖርት ተሳትፎም ከፍ ሊልና ወደ ቀድሞ ቦታው ሊመለስ ይገባል። የሠራተኛው ስፖርት ከተለያዩ ፌዴሬሽኖች ጋር በመነጋገርም መዋቅርም ሆነ የተለያዩ አሠራሮች ለሠራተኛው ምቹ ሆነው እንዲቀረፁ መደረግ ይኖርበታል። የኢትዮጵያ ስፖርት ዳግመኛ በሠራተኛው ላይ የበለጠ ትኩረት አድርጎ የሚሠራበት መንገድም መፈጠር ይኖርበታል። ይህም ብቻ ሳይሆን የሠራተኞች ወይንም የፋብሪካ ቡድኖች ጋር ወርዶ መነጋገር ተገቢ እንደሆነ ገነነ ያክላል። በተጨማሪም በሠራተኛው የስፖርት ውድድር ላይ ከሠራተኛው ውጪ በምንም ዓይነት ሁኔታ ሌሎች መሳተፍ የለባቸውም የሚለው አቋም ሊፀና ይገባል። ሠራተኛውን ወደ ቀድሞው ተጽዕኖ ፈጣሪነት ስፍራው ለመመለስ መሥራት ይቻላል። ምክንያቱም ሠራተኛው ቀድሞውንም በስፖርቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ነበረና።

 ቦጋለ አበበ

 

Published in ስፖርት
Saturday, 13 January 2018 19:59

ያልተከፈተው ስጦታ

እአአ በ1970 ነው በካናዳ ኤድመንተን ከተማ። አድርያን ፒርስ የተባለ የ17 ዓመት ወጣት ከሴት ጓደኛው ጋር ከተቀጣጠሩበት ቦታ ይሄዳል። የገና በዓል ሰሞን ነበርና የጓደኛው ጥሪ ከወትሮው የተለየ ይሆናል ብሎ አልጠበቀም። ነገር ግን አልነበረም፥ «አድሪያን...እኔና አንተ ከዚህ በኋላ አብረን መቀጠል አንችልም» አለችው፤ መርዶ!የሚወዳት ብሎም ቀሪ ዘመኑን አብሯት ሊያሳልፍ ያለማት ልጅ ነበረችና ልቡ ተሰበረ። እርሷም ልቡን ሰብራ ብቻ አልሸኘችውም፥ የገና ስጦታ ሰጠችው፤ በወርቃማ ሰማያዊ የስጦታ መጠቅለያ የታሸገ የመለያያ ስጦታ። ሰባራ ልቡን ባይጠግንለትም ስጦታውን ይዞ ወደቤቱ አቀና። በቤቱም ከገና ዛፉ ስር ከተከመሩ ስጦታዎች መካከል አኖረው።

ይህ እውነተኛ ታሪክ ነው፥ አላለቀም። ወደታሪኩ ዘልቀን ከመግባታችን በፊት አንድ ነገር ትዝ አለኝ፥ መቼም በአገራችን ኢትዮጵያዊ የሆነ የገና በዓል አከባበር ስርዓት አለ። ግን እንደው እኚህ አውሮፓውያን ከገና ዛፋቸው ይልቅ የስጦታ መለዋወጥ ባህላቸውን ቢያጋቡብን አትመኙም?
ወደነገሬ ልመለስ፥ አድሪያን ያንን ስጦታ በቤታቸው ካለው የገና ዛፍ ስር አስቀመጠው። ቤተሰቦቹ ስጦታቸውን ሲከፍቱ እርሱ ግን የተሰጠውን ስጦታ ሳይከፍተው ቀረ። አንድ ጊዜ ብቻም አይደለ፥ ተከታትለው በመጡት ዓመታት በገና ዛፍ ስር ካሉ ስጦታዎች ጋር ያስቀምጠዋል፤ አይከፍተውም።
47 ዓመታት አለፉ። አሁን የስጦታ ማሸጊያው ቀለሙ ደብዝዟል። አድርያንም ባለትዳርና የልጆች አባት ሆኗል። ልጆቹም በየዓመቱ በገና ዛፋቸው ስር የሚያዩት ግን ተከፍቶ የማያውቀው ስጦታ ግራ ያጋባቸዋል፤ አባታቸው እንዲከፍቱት ፈቅዶላቸው አያውቅምና። ባለቤቱ የልጆቹን ሁኔታ በማየት ያለተከፈተው ስጦታ የገና ዛፉ ስር እንዳይቀመጥ ለባሏ ነግራ አስቆመችው።
በየዓመቱ ስጦታውን እያየ መልሶ ማስቀመጡን ቀጠለ። አድርያን ስጦታውን ለመክፈት ከአንዴም ሁለቴ እጁ ተነስቶ እንደነበር አይደብቅም፥ በተለይ ወረቀቱ የተያያዘበት ፕላስተር አንዳንድ ቦታ ላይ አያይዞ መቆየት አለመቻሉ ፈትኖት ያውቃል። ግን ስጦታውን ሸፍኖ እንዲያቆይ ከታዘዘ ማሸጊያ ፕላስተር ይልቅ «አልከፍተውም» ያለው አድርያን ለሃሳቡ ታምኖ ቆየ። መጽሐፍ ይሆን? የእርሷ ፎቶስ ቢሆን? ቸኮላትም ይሆናል...አድርያን አያውቅም።
«መጀመሪያ ስጦታውን ሳልከፍት የቆየሁት በድጋሚ አብረን ልንሆን እንችላለን በሚል ተስፋ ነበር መሰለኝ፤ ስንታረቅ አብረን እንድንከፍተው አስቤ። አሁን ግን ስጦታውን ማየትና በማየት ብቻ ደስ መሰኘት ሳይለምድብኝ አልቀረም» ብሏል። በነገራችን ላይ ምንም እንኳ በልጆቿ «እንክፈተው» ጥያቄ ምክንያት ስጦታው ከገና ዛፍ ስር እንዳይደረግ ያዘዘች ቢሆንም፥ ባለቤቱም በነገሩ እንደ እንግዳ የስጦታውን መከፈት ትጠብቃለች። ቅናት? ኧረ በጭራሽ! የተባረከች!
አርባ ሰባት ዓመት? አድሪያን ስጦታውን ከሶስት ዓመታት በኋላ፥ ማለትም ስጦታው ከተሰጠው ከሃምሳ ዓመታት በኋላ ሊከፈተው አስቧል። በመክፈቻ ስነስርዓቱም ላይ ሰዎችን በመጋበዝ ለአንድ እርዳታ ተቋም ገቢ ለማሰባሰብ የሚያስችል ዝግጅት አስቧል። ምንአልባት ልቡን ሰብራ ስጦታ የሰጠችው ሴት ብትገኝም የዝግጅቱ ተሳታፊ ትሆናለች ብሏል። ይህን ታሪክ ሲቢሲ የተባለን የዜና ምንጭ ዋቢ አድርጎ ኒውሰር በድረገጹ አስነብቧል። እንግዲህ የዛሬ ሶስት ዓመት ሰው ይበለና!

ሊድያ ተስፋዬ

Published in መዝናኛ
Saturday, 13 January 2018 19:57

የማይደገፍ ድጋፍ

አገሬ ውስጥ ያለ የአንድ እግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች ናቸው፤ ህዝብ በማመላለስ ወገቡ የጎበጠ የሚመስል በቅጽል ስሙ «ቅጥቅጥ» የሚባል የሕዝብ መኪና ውስጥ ይዘላሉ። ሁኔታውን ላይ መኪናው ራሱ ዝላይ የያዘ ነው የሚመስለው። በዛ ላይ በመተንፈሻ መስኮቶቹ በኩል አንገትና እጃቸውን ብቅ ብቅ ያደረጉቱ ጎኑን ይደበድቡታል። ጉዱን አላየ የመኪናው ባለቤት!
በአገሬ ላይ ከሁሉም ከሁሉም «አገሬን አልተውም» ያለ ነገር ቢኖር ኳሳችን ይመስለኛል። በቃ! አቅሙም፣ ኃይሉም፣ ስልጣኑም፣ ብርታቱም... ሁሉም በጓዳ ነው፤ በአገሩ። ከሄደ እንኳን ደርሶ አገር አይቶ ምልስ ይላል። እንደ አገሬ ኳስ ጨዋ ወዴት አለ?
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ወጣት እንደሆኑ የሚገመቱ ሰዎች ያንን መኪና እንዲያ ሲዘሉበት አያቴ ብርድልብስ ለማጠብ ስትፈልግ በእግራችን እንድናሽላት የምታሰማን ተማጽኖ ትዝ አለኝ። ለኳስ እንዲህ እንደሚዘለል ብታውቅ ምን ትል ነበር? «እንኳን ለሚያሞቀኝ ብርድ ልብስ ቅስም ለሚሰብር ኳስ ትዘሉ የለምን?» ብትልስ?
እንዲያ ከሚጨፈርበት የሕዝብ መኪና አጠገብ ነው አንገቱን ደፍቶ በትህትና የሚንቀሳቀስ የሚመስል እኛ የተሳፈርንበት ታክሲ የቆመው። መንገዱ ተዘጋግቷል፤ ረዳቱ ከፊት የሚጠብቀን ለማየት አንገቱን እንደኤሊ ራስ በመስኮቱ ሲያወጣ ከሚዘለልበት መኪና ውስጥ የሚወጣው ድምጽ ጎልቶ ተሰማ። «አሸንፈው መሆን አለበት!»
«ምን በልተው ነው ግን እንዲህ የሚጨፍሩት!» አለ አንዱ፤ የመኪናው ባትሪ ላይ በትርፍ ተጭኖ የተቀመጠ ጎልማሳ። ሰው መዝገቡ ባለበት ልቡ በዛ ይኖራል፤ በልቡም የተመላለሰና ከዛ የተረፈውን አንደበቱ ይናገራልና ያ ሰው ያልተሞላ የሆድ ጉዳይ እንደሚያሳስበው ገመትኩ።
«የሆነ ነገርማ ተከፍሏቸው መሆን አለበት» ሌላው አከለ፤ ፈገግ አልን። ከሕዝብ ማመላለሻ መኪናው የሚሰማው ድምጽ፣ ዝላዩ፣ የመንገዱ መጨናነቅ እንደቀጠለ ነው። ሁላችንም ከመንገዱ መዘጋጋት ይልቅ የመኪናዋ እንቅስቃሴ አሳስቦንም፣ አሳዝኖንም ሁኔታውን እየተከታተልን እንመስላለን፣ ከውጪ ሆኖ የሚያየን ቢኖር።
በአንድ ወገን ሰው ከእንግሊዝ የእግር ኳስ አጨዋወትና ከተጫዋቾቹ የእለት ከዕለት ኑሮ መለስ ብሎ የራሱን ኳስ ማየቱ ደስ የሚያሰኝ ነው፤ ይደገፋል። በስታዲየም ተገኝቶም ጨዋታዎችን ተመልክቶ፥ የሚያደንቀውን አድንቆ በሚያበሳጨው ተበሳጭቶ ወደየመጣበት መሄዱም እንዲሁ ይደገፋል። የማይደገፍ አንድ ነገር አለ፤ አደጋገፉ። በተለይ ወሳኝ፤ የደርቢ የሚሏቸው ጨዋታዎች በሚኖሩበት ጊዜ ስታዲየም አካባቢ የሚንቀሳቀስ ሰው «ዛሬ የእነ እገሌ ጨዋታ አለ አሉ፤ በጊዜ ወደቤት» ይላል። አሃ! ለምን? በጊዜ ወደቤት መግባት መልካም ሃሳብ ሆኖ ሳለ፤ መሳቀቁ ለምን ነው?
ከዛ በላይ ደግሞ ሴቶች፤ እንዴ? ለከፋው በዛ! በተለይማ አነስ ባለ መኪና ሰብሰብ ብለው የቡድኑን መለዮ እያውለበለቡ ባለፉበት መንገድ ሴቶችን የሚያሳቅቁ፤ በዛም የማያፍሩ አሉ። ይሄን የገጠማት ታውቀዋለች፥ አንዴ በጅምላ ሆ ብለው ያለፈቃድ ሰውን ሲናገሩ ቅር ያሰኛል፤ አግባብ አይደለም፤ አይደገፍም። የሚደበደቡትን መኪናዎችማ ብትተዉት ይሻላል፤ የመኪናም ጡር አለው የሚልልን ነው ያጣነው።
በአትሌቲክስ ውድድር ስታዲየሞች ጭር እንደሚሉ ጓደኛዬ ነገረችኝ፣ መቼም እንግሊዞች ለኳስ እንዲያ የሚሆኑት ኳስ ስለሚችሉ ነው፤ እኛ የምንችለው ኳስ ሳይሆን ሩጫ እንደሆነ አስመስክረናል። ግን በዓለም መድረክ የሚታይ ካልሆነ በቀር ሩጫን ጉዳዬ ብሎ የሚያይ የለም። የአገራችንን ኳስ አድናቂዎች ካላችሁ አትቀየሙኝና...ሌላው ይቅር! እንደው ለኳስ የሚወጣውን ወጪ ያህል ለአሎሎ ውርወራና ከፍታ ዝላይ ቢወጣ ውጤታማ አንሆንም ነበር?
«መጨረሻው ነው እሙዬ!» የታክሲው ረዳት የሃሳቤ ርዝመት የገባውና አቀማመጤ ደስ ያላለው መሰለኝ። የታክሲ ረዳቶችን የማደንቃቸው ለዚህ ነው «ውረድ!» ወይም «ውረጅ!» አይሉም፤ «መጨረሻ...» ሲሉ እንወርዳለን። «ይቅርታ!» አልኩኝ በታክሲ ውስጥ እኔ ብቻ መቅረቴን ሳስተውል፤ ወረድኩ።
መንገዱ ለእግረኛም ተጨናንቋል። መገናኛ አካባቢ እንደዚህ ነው፣ በአዘቦቱም በበዓሉም ይጨናነቃል። በእርጋታ፣ ላለመረገጥም ላለመርገጥም በመጠንቀቅ እልፍ እልፍ እያሉ ነው መሄድ። ዞር ብዬ አንዳች ቃላቱ በግልጽ የማይሰማ ዘፈን የሚሰማበትን መኪና ተመለከትኩት። «አይደክማቸውም እንዴ?!» ድካም በልቤ ነበርና ድካምን አሰብኩ።
ዓይኔን ከመኪናው ላይ ወደመንገዴ ስመልስ ከአንድ ወጣት ልጅ ጋር ተገጣጠምን፤ በፈገግታ ተያየን። ያሰብነው አንድ ሃሳብ ይመስላል ምን እንደሆነ ግን አላውቅም። «የጊዮርጊስ ደጋፊ ነሽ?» አለኝ። «አይይ...እርሱ ይደግፈኝ እንጂ!» መለስኩለት። «የቡና?» መልሶ ጠየቀ፥ ለምን አስፈለገው? «በአጋጣሚዎች አያለሁ እንጂ ድጋፍ ላይ እንኳ የለሁበትም» አልኩት።
ፈገግ ብሎ አየኝ። «እኔ አሁን ከስታዲየም ነው የመጣሁት፤ ጥሩ ጨዋታ ነበር። ከጨዋታው ግን ድጋፉ ሳይበዛ አልቀረም» አለኝ። የደጋፊዎቹ ሁኔታና አጨፋፈር ምን ዓይነት ድል ያመጣው እንደሆነ ለማወቅ መጓጓቴ ያወቀብኝ መሰለኝ፤ ልጠይቀው ይሆን?
«...ስሜታዊ ስንሆን ደስታችንን የምንገልጽበት መንገድ እኛን እንጂ ሌሎችን እንድናስብ አያደርገንም፤ ይህ የእኔ መላምት ነው። ድምጻቸው፣ መኪና መደብደባቸው፣ ዝላያቸው፣ እንዲህ ተሰብስበው ደግሞ ሲላከፉና ሴቶችን ሲናገሩ... ያጋጥመኛል። ኳስ ነው፤ ስታሸንፍ ደስ ይላል፤ ግን አደጋገፍም ስርዓት ያለው ይመስለኛል» አልኩት፤ መልስ ግን አልሰጠኝም።
«አሸንፈው ነው?» ጠየቅሁ
«አይ!» መለሰልኝ፤ በመገረም አየሁት
«ታዲያስ?»
«ያው አቻ ወጥተው ነው?»
«አቻ? አቻ መውጣታቸውና አንድ ነጥብ ማግኘታቸው ልዩነት የሚያመጣ ዓይነት ነው? ማለቴ...» ጥያቄዬ አላለቀም።
«ምንም፤ ያው ጨዋታው ይቀጥላል፤ ነጥብ ተጋርተው የዛሬው አበቃ ነው» ነገረኝ።
«ያሸነፉ መስሎኝ ነበር፤ ይገርማል...ታዲያ ስንት ለስንት ወጥተው ነው?» በጥያቄዬ ሳላሰለቸው ቀረሁ ብላችሁ ነው «ማንም አላገባም፤ ባዶ ለባዶ» አለኝና ፈገግታውን ሳያጎድል እጁን አውለብልቦ ተሰናብቶኝ ሄደ። አቻ? ያውም ባዶ ለባዶ? ምን ትላላችሁ፣ እንግዲህ በነገር ሁሉ ደስ መሰኘት ይገባል ብለን እንውሰደዋ! ይህ ባይሆን ይደገፋል!

ሊድያ  ተስፋዬ

Published in መዝናኛ
Saturday, 13 January 2018 19:55

ሴቶች በሁለንተና

‹‹ይህማ የወንዶች ስራ ነው ሴት ይህን ማከናወን እንዴት ይቻላታል›› የሚሉና መሰል ኋላቀር አመለካከቶች እንደነበሩ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡ ዛሬም እንደትናንቱ በአትችልም መንፈስ የታጠሩ ብዙዎች መኖራቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች ብልጭ የሚሉ ማሳያዎች ያረጋግጣሉ፡፡ ይህንንም አልፋ የተሻለ ውጤት ስታስመዘግብ የታየች ሴት ‹‹ወንዳታ›› የሚል የማበረታቻ ታገኛለች፡፡ይህም የወንዱን ስራ መስራት ቻልሽ የሚል መሆኑ ነው፡፡ከአባባሎቻችን ጀምሮ «ሴት አትችልም » አይነት ማሳያዎች ማንሳት ይቻላል፡፡
ኋላ ቀር አመለካከቶች ሳይሸብባቸው በርካታ ተግባራትን ያከናወኑ ጠንካራ ሴቶች ግን የወንዶችን የበላይነት ከሚያንፀባርቁት ግለሰቦች እናትነት ጀምሮ በአደባባይ እስከሚታወቁት በየቤታችን ያሉት የሁላችንም ተምሳሌት ናቸው። ጦር ሜዳ ገብተው ከትግል ቀያሽነት እስከ ድል አድራጊነት ትልቅ ሚና ያላቸው ሴቶች ሁሌም በዓይነ ህሊናችን እንደተፃፉ ይኖራሉ፡፡ በተለይም በሰላም ማጣት ዙሪያ ዋነኛ ተጠቂዎችም ሴቶች ናቸውና አሁን አሁን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ብልጭ ድርግም የሚለው የሰላም እጦትና አለመረጋጋት ሲያጋጥም ሰላም እንዲሰፍን ወጣቶችን በመምከር፣ ልጆቻቸውን በመያዝና የሰላም ማጣት የሚያስከትለውን ችግር በማሳወቅ ትልቅ ሚና እየተወጡ ናቸው። ሴቶች የሚጠበቅባቸውን ሚና በተገቢው መንገድ እንዲወጡ ምን እየተሰራ ነው ስንል ከአዲስ አበባ ኢህአዴግ ሴቶች ሊግ ሊቀመንበር ወይዘሮ የሺ ወልዴ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እነሆ፡፡
ምን ታሰበ?
የሴቷን ተጠቃሚነት ሲባል በውስጡ በርካታ ሀሳቦችን አቅፎ ይይዛል፡፡ በተለይም የሴቷን ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ተሳትፎዋን በማሳደግ ተጠቃሚነቷን ማረጋገጥ ትኩረት የሚሰጠው ተግባር ነው፡፡ በዚህም በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ እንዲሁም የሴቶችን ተጠቃሚነት ዕውን ለማድረግ ሰላም ቀዳሚ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑ አይካድም። የአገሪቱ ፖሊሲ ከመልካም አስተዳደርና ከዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጋር ተያይዞ ሰላም፣ልማትና ዴሞክራሲ የማይነጣጠሉ ጉዳዮች እንደሆኑ በግልፅ ያስቀምጣል፡፡
ልማትን ለማምጣት የተረጋጋ ምቹ ሰላማዊ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ ሴቶች ሊኖራቸው የሚችለው ፋይዳ ጉልህ ነው፡፡ በመሆኑም አልፎ አልፎ በአገሪቱ እየታዩ ያሉትን ያለመረጋጋት ችግሮች ለማቃለል የሴቷን አቅም ማጎልበትና ተሳትፎአቸውን ማሳደግ ላይ እየተሰራ ይገኛል፡፡
በህገመንግስቱ መብት የተሰጣቸው ሴቶች እንደማንኛውም ዜጋ የመደራጀት መብትም አልተነፈጋቸውም፡፡ እናም ይህች ሴት ከማጀት ወጥታ ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ያላቀቃት ይህ ስርዓት የጀመራቸው በርካታ የልማት ግስጋሴዎች በፀረ - ሰላምና ፀረ- ልማት አካላት እንዳይደናቀፍ የበኩሏን መወጣት ይኖርባታል፡፡ በመሆኑም ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሴቶች ያላቸው ሚና ምንድን ነው? በሚልና በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ከደረሰችበት የዕድገት ደረጃም ጋር ተያይዞ ሴቶች ምን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው መመካከር ይገባል፡፡ ሴቶች እንደ እናት፣እህት፣ሚስት እንዲሁም ልጅ በአጠቃላይ ሰላም ላይ የጎላ ስራ መስራት ይገባል። እናም በዚህ ረገድ ምን ሚና ይኖራቸዋል? እንዴትስ ነው በጋራ ተቀናጅቶ መስራት የሚቻለው በሚለው ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ያግዛል።
የሴቷን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ያረጋገጠው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ስርዓትና ሴቶች የማይነጣጠሉ ናቸው ከተባለ ይህ ስርዓት በምን መንገድ መቀጠል አለበት? ለሌሎችስ እንዴት ግንዛቤ መፍጠር ይቻላል? የሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ቅድሚያ አደረጃጀቱ መጠናከር ይኖርበታል።
በሶስት ወራት ውስጥ በሚፈጠሩ የተለያዩ መድረኮችም ያሉ ክፍተቶችና ጥንካሬዎች ይለያሉ። ይህም ጥንካሬው ወደ ሌሎች የሚሰፋበት ጉድለቶችም በየመድረኩ ተፈተው የሚኬድበት ሁኔታዎችንና ዕድሎችንም ያመቻቻል። ቀድሞ ሲደረግና በክፍተት ይነሳ የነበረው የድጋፍና ክትትል አግባብ እንዴት መቀጠል እንዳለበት በመፈተሽም መፍትሔ ያመላክታል። በሶስት ወራቱ ውስጥም ስራውን እንዲያስተባብሩ የተለዩት ሴቶች ከሴቷ ጋር አብረው እየዋሉ ሴቶች ያለባቸውን ችግር እንዲሁም የተስተካከሉ ጉዳዮችን ይለያሉ። በዚህም የሴቶች የመልካም አስተዳደር ችግርና ተጠቃሚነት ላይ ያሉ ተግዳሮቶች ምን እንደሆኑ በቀላሉ ለማወቅና ደረጃ በደረጃ መፍትሄዎች ለመስጠት ይረዳል።
ተጠቃሚነት
መንግስት የሴቷን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች ተከትሎ ሰፊ ጉድለቶች ይስተዋላሉ፡፡ ምንም እንኳን ለውጦች እንደመጡ አመላካች የሆኑ የብርሃን ፍንጣቂዎች ቢኖሩም በሚፈለገው ልክ ግን አይደለም፡፡ስለሆነም እነኚህን ችግሮች ታች ድረስ ታግሎ ለማስተካከል መስራት ይጠይቃል፡፡ለዚህም ችግሮችን በአቅም ታግሎ ለማስተካከል የሚያስችል ቁመናን ለሴቷ ማላበስ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡በዋናነትም በአቅም ግንባታ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ከተፈለገ ታች ካለው መዋቅር መጀመር ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም የነበሩ ክፍተቶችን በመዝጋት ከሴቶች ጋር ተቀራርቦ የተሻለ ስራ መስራት ይቻላል፡፡
ድሮና ዘንድሮ
እያንዳንዱ ተግባር ያለ ሴቶች ተሳትፎ ዕውን ማድረግ አዳጋች ነውና ቀደም ሲል በትግሉ እና በአሁኑ ወቅት ያላቸው ሁለንተናዊ ሚና ሲታይ በርካታ ለውጦች አሉ፡፡ ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ ሴቶች ከወንዶች እኩል መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ አሁንም ለስርዓቱ መቀጠል ያላት ቁርጠኝነት ከምንም ጋር የሚነፃፀር አይደለም፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ሰላም ሲታወክ የመጀመሪያው ተጠቂ ሴቷ እና ህፃናት ናቸው፡፡
ፖሊሲው፣ስትራቴጂው እና ህገ መንግስቱ ለሴቶች በፈጠሩት ምቹ ሁኔታዎች ሴቷ ተጠቃሚነቷን አረጋግጣለች፡፡ይህ ማለት ግን ሴቶች በአሁኑ ወቅት ምንም ጥያቄ የላቸውም ማለት ሳይሆን በተለያዩ መድረኮች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ተገቢነት ያላቸው ናቸው፡፡ነገር ግን ለበርካታ ህዝባዊ ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጠ በመጣው በዚህ ስርዓት እንደሚመለስ ተስፋ አላቸው፡፡
በአሁኑ ወቅት የመልካም አስተዳደር፣ የተጠቃሚነት፣የቢሮክራሲ ማነቆዎችና የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ አለመደፈቁ ሴቷ በሚፈለገው ደረጃ ትርጉም በሚያመጣ መልኩ ተሳትፎ እንዳታደርግ ያሳደረው ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ይህንን ለማድረግ የሴቷ ሚና ቀላል የሚባል ባለመሆኑ የመንግስትም ሆነ የሚመለከተው አካል ሁሉ ድጋፉን ሊነፍግ አይገባም፡፡ የሴቷን ትግል ደግፎ ዳር ማድረስና ጥያቄዎቿን በተገቢው ደረጃ መመለስ ይኖርበታል፡፡የህዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሴቶችም በተመሳሳይ በራሳቸው ፀድተው ሌላውን ለመታገል በቁርጠኝነት መግባት አለባቸው፡፡
ማነቆዎች
ሊጉ የተቋቋመበት ዓላማ የሴቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባሻገር ሴቷ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳታፊነቷን በማሳደግ ሚናዋን እንድትወጣ ለማድረግ ነው። ሆኖም ከሚሰራው ስራ ጋር ተያይዞ ችግሮች ይታያሉ። ኢህአዴግ ሁሌም ቢሆን ችግሮችን ወደ ውስጥ የሚያይና አፋጣኝ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን እያስቀመጠ የመጣ ድርጅት ነው።
በጥልቅ ተሃድሶ መድረኩም በርካታ ችግሮች ተነቅሰው ወጥተዋል። ባለፈው ዓመት በተደረገው ተሃድሶ ከተለዩት ችግሮች ዋነኛው የሴቷን ፖለቲካዊ አቅም ማሳደግ ላይ አለመሰራቱ እና የአቅም ውስንነት ጉዳዮችም አሉ። ለዚህም ድርጅቱ የገመገማቸው በከተማዋ ያለው የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ የበላይነት መያዝ ለአብነት ይጠቀሳል።ይህንን ለመቅረፍ ትልቁ አቅም የሊጉ መዋቅር ነው።ይሁን እንጂ የሊጉ መዋቅር ችግሩን መድፈቅ አልተቻለውም። በዚህም ትግል እየተደረገ አለመሆኑ ተገምግሟል።
ችግሮችን ለማስተካከል የፖለቲካል ብቃትና ቁርጠኝነት እንዲሁም ራስን ከዚህ ነፃ አድርጎ መታገልን ይጠይቃል።በዚህ ላይ በሙሉ አቅም እየተገባ አይደለም።እንዲሁም በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በከተማዋ እንዳሉ ተገምግሟል፡፡እነኚህ ችግሮች እየተፈጠሩ ያሉትም የሊጉ መዋቅር ባለበት ደረጃ ታግሎ ማስተካከል ባለመቻሉ ነው። ይህም የሚያመላክተው ሴቷ ከታች እስከ ላይ መታገል የሚያስችላቸው አቅም መገንባት ላይ ክፍተት በመኖሩ ነው።
የትኩረት አቅጣጫዎች
ቀደም ሲል ስራ በመረጣ ላይ የተመሰረተ የነበረው አመለካከት አሁን መሰበሩን የሚያሳዩ ተግባራት አሉ። ሴት ከቤቷ የማትወጣና በአደባባይ አንገቷን ቀና አድርጋ መናገር የማትችል ነበረች፡፡በአሁኑ ወቅት ይህ ሁሉ ተቀይሮ ጠያቂና ሞጋች የሆኑ ሴቶች ተፈጥረዋል፡፡ ሊጉም አመለካከት ቀረፃ ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል፡፡ በአሁኑ ወቅት ቀድሞ ይታይ የነበረው ስራ ጠል አመለካከት ተቀይሮ ስራ ይቅረብልኝ የሚሉ ሴቶችን መፍጠር ተችሏል። ከዚህ አንፃርም ሴቶችን የማብቃት ዕቅዱ አመርቂ ለውጥ ታይቶበታል። በዚህም ከነበሩበት ሁኔታ ወጥተው ራሳቸው በኢኮኖሚ ከመቻል ባሻገር ለብዙዎች የስራ ዕድል የፈጠሩም አልጠፉም። ነገር ግን የመጣው ለውጥ አበረታች ቢሆንም አሁንም አቅምን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል፡፡
ሴቶች ተደራጅተው እንዲታገሉ ይጠበቃል፡፡ ባለፉት 10 ዓመታትም በርካታ ውጤቶች ተመዝ ግበዋል፡፡መንግስት ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የያዛቸው አቅጣጫዎች እንዲተገበሩ ያስቀመጣቸው ብሎም ሊጉ የሚያቅዳቸው ዕቅዶች መሬት ላይ ወርዶ ተጠቃሚ ማድረግ እንዲችሉ ይደረጋል፡፡በመዋቅሩ ውስጥ ምንም ስራ የሌላት ሴት እንዳትኖር በተመሳሳይ በአደረጃጀቱ ያልታቀፉ ሴቶችንም ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል።ይህም ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም መረባረብ ይኖርበታል።

ፍዮሪ ተወልደ

Published in ማህበራዊ

«ጥቃቅንና አነስተኛ ሲባል እንደምንገምተው አይደለም፤ በርትቶ ለሠራ ብዙ ጥቅም አለው። እኔ በወር 500 ብር እየላኩ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ልጅ አስተምሬ አስመርቄያለሁ። ወደእዚህ ሥራ ባልገባ ኖሮ ምን አደርግ እንደነበር አላውቅም» የሚሉት በድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አይናለም ገዛኸኝ ናቸው። ወይዘሮ አይናለም ወደ ሥራው የገቡትበንም አጋጣሚ እንዲህ ያብራሩታል። ከስድስት ዓመት በፊት በቀበሌ አማካይነት ጥሪ ተደርጎ መደራጀት ስንጀምር በወር 20 ብር በመቆጠብ ነበር። ከወራት በኋላ ለሥራዬ መነሻ የሚሆን ገንዘብ በብድር ተሰጥቶኝ መሥራት ከጀመርኩ በኋላ ግን ቁጠባዬም በየወቅቱ እያደገ መጥቷል።በአሁኑ ወቅት 130 ሺ ብር ካፒታል ማስመዝገብ ችያለሁ። በተለያዩ ጊዜያት የካይዘን ስልጠና ስለተሰጠን እሱን መሰረት እያደረግን ነው የምንሠራነ ው፤ በበኩሌ ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣት አስችሎኛል። ሰባት ቤተሰብ አለኝ በልተን ጠጥተን ከማደር በላይ የተለያዩ ወጪዎችን እየደፈንኩ ለመኖር አስችሎኛል። ቋሚ ገበያም ሆነ የመሸጫ ቦታ ባይኖርም ጥሩ ሥራ ከተሠራ ገዢ አይጠፋም። በቀጣይ ልጆቼም ከእኔ ጋር እንዲሠሩ የማድረግ ሃሳብ አለኝ። ከእኔ በታች ያሉትንም በአቅሜ ለማሰልጠን አስባለሁ። ይሄን ሁሉ ለማድረግና ካፒታሌን ለማሳደግ እየሠራሁ ነው። እስካሁን ከመንግሥት ይደረግ የነበረው ድጋፍ እንደሚቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉ ይናገራሉ። 

«ሥራ አጦችን በጥቃቅንና አነስተኛ የሚያደራጁ በየቤቱ ዞረው ሲመዘግቡ በልብስ ስፌት ለመሳተፍ ተመዘገብኩ። ሥልጠናም ወሰድኩ። አሁን ከመንግሥት የመሥሪያ ቦታ ተረክቤ መሥራት ጀምሬያለሁ» ያሉን በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሉባባ ሲራጅ ናቸው። ወይዘሮ ሉባባ በ2006 ዓ.ም ከፌዴራል የከተሞች የሥራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲው በተደረገላቸው ድጋፍ በ2ሺ 500 ብር የልብስ ስፌት ሥራ ጀመሩ፡፡ «መጀመሪያ 3ነጥብ5 ካሬ ላይ ነበር ሥራዬን የጀመርኩት ከዛ በኋላ ካፒታሌ እያደገ በመምጣቱ ከነበረኝ አንድ ማሽን በተጨማሪ ሶስት አስገባሁ። ሁለት ሠራተኞችም ቀጠርኩ። መንግሥት ይሄንን በመመልከት 30 ካሬ ተጨማሪ ቦታ ሰጥቶኝ ሥራዬን ለማስፋፋት ችያለሁ» ይላሉ።
በአሁኑ ሰዓት አልጋ ልብስ፣ የትራስ ልብስ፣ የሶፋ ጌጦች፣ የወጥ ቤት ጓንትና የአዋቂ አልባሳትን በማምረት ላይ ይገኛሉ። ቀደም ሲል ያልነበራቸውን ሙያ ቀስመው መሥራት በመቻላቸው ኑሯቸውን ለውጠዋል። ለልጃቸው የትምህርት ቤት እና ለራሳቸውም የሚያስፈልጋቸውን ወጪ ሁሉ መሸፈን ችለዋል። ይሁን እንጂ ዛሬም ለሥራቸው በተለይም የተሻለ ገቢ ማግኘት እንዳይችሉ እንቅፋት የሆነባቸው የገበያ ትስስር አለመኖር መሆኑን ይናገራሉ። ብዙ ጊዜ ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅና ገቢም ለማግኘት የበዓል ባዛርን መጠበቅ ይገደዳሉ። በቀጣይ የተሻለ ምርት በማምረት ከውጪ የሚመጡትን አልባሳት በአገር ውስጥ ለመተካት ዕቅድ አላቸው። ወይዘሮ ሉባባ በአሁኑ ወቅት ካፒታላቸው 100ሺ መድረሱንም አልሸሸጉም።
ከሶስት ዓመት በፊት ሥራ የጀመረችው በ15 ሺ ብር ካፒታል ነበር፤ ከሶስት ዓመት በኋላ ዛሬ ካፒታሏ 100 ሺ ማድረሱን ያጫወተችን ደግሞ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ወይዘሪት ማንለኝ አምዲሳ ናት። ወጣቷ እንደምትለው ተቀጥሮ መሥራት አስቸጋሪ ነው። በግል መሥራት ግን ራስን ለማሻሻልና የበለጠ ለመሥራት እድሉ ይኖራል። በተጨማሪም ቅጥረኛ ሲኮን የራስን ሀሳብ አመንጭቶ አዲስ ነገር ለመፍጠር አይቻልም። በግል ሥራ የራስን ብቻ ሳይሆን የደንበኞቼንም ፍላጎት በማዳመጥ አዳዲስ ነገር መሥራት ይቻላል።
«በአሁኑ ወቅት በኑሮዬም በምሠራው ሥራም ደስተኛ ነኝ ፤ ወደእዚህ ሥራ ከመግባቴ በፊት ከነበረኝ የተሻለ ህይወት እየመራሁ እገኛለሁ። ከራሴም አልፎ በስሬ ሁለት ሠራተኞችን መቅጠር ችያለሁ። ወደፊት የተሻለ ቦታ ለመድረስና ፋብሪካ ለመክፈት አላማ አለኝ። አሁንም ቢሆን ግን የመንግሥት ድጋፍ ሊለየን አይገባም። መንግሥት በተሻለ ምርታችንን የምናስተዋውቅበትንና የምንሸጥበትን ሁኔታ ቢያመቻች እንዲሁም ባዛሮችን በተደጋጋሚ ቢዘጋጅ፤ አልያም ከተቋማት ጋር የገበያ ትስስር ቢፈጠር በብዛት አምርቶ ለመሸጥ እድሉ ይኖራል ፤ ካፒታላችንንም የበለጠ ማሳደግ እንችላለን» ስትል ትናገራለች።
በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ አስር ነዋሪ የሆነው ወጣት ዮሐንስ ጎበና በበኩሉ መደራጀቱ ከዚህ በፊት ሲሠራ ከነበረው የጉዳይ ማስፈጸም ሥራ የተሻለ ጥቅም እንዳስገኘለት ይናገራል። ተደራጅቼ ሻማና ጧፍ ማምረት የጀመርኩት ከአምስት ዓመት በፊት ነበር። ከዛ በፊት ቋሚ ሥራ የለኝም የምሠራው ጉዳይ የማስፈጸም ስራም አስተማማኝ አልነበረም። አሁን ግን የገበያ ትስስሩ አስቸጋሪ በመሆኑ በቂ ገቢ ባላገኝም ውሎ መግባቱና ስራ አለኝ ማለቱ በራሱ ትልቅ ነገር ነው። ለወደፊት የተጠናከረ ስራ ሰርቼ ለኔም ለልጄም የሚሆን ጥሪት የመቋጠር ተስፋ ሰንቄያለሁ።መቼም ቢሆን ተቀጥሮ የመስራት አላማ ስለሌለኝ ሁኔታዎች እስከተመቻቹልኝ ድረስ ይህንንኑ አጠናክሬ የምቀጥል ይሆናል።ለቀጣይ ግን ጥቃቅንና አነስተኛ የገበያ ፈጠራውን ነገር ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት። የኛ ብዙ ማምረት ብቻውን ዋጋ የለውም ። በአሁኑ ወቅት እየሰራን ያለነው ማምረት ከምንችለው በጣም ጥቂት ብቻ ነው።አቅማችን ብዙ ማምረት የሚያስችለን ቢሆንም ካልሸጥነው ዋጋ የለውም።ስለዚህ እንዴት ገበያ ማፈላለግ እንደምንችል ስልጠና ቢሰጥ ልፋታችንን ውጤታማ ማድረግ እንችላልን ይላሉ።
በደብረዘይት ከተማ ነዋሪ የሆነችውና የቆዳ ውጤቶችን በማምረት የተሰማራችው ወጣት ራሄል አለሙ ከቤተሰቧ ጋር የምትኖር ቢሆንም በብዙ ነገሮች ራሷን መደገፍ መቻሏን ትናገራለች። በኑሮዬ ላይ የሚታይ ለውጥ ማምጣት ችያለሁ ስትል ለራሷ ምስክርነት ትሰጣለች።
«ምናልባትም ተደራጅቼ ወደእዚህ ሥራ ባልገባ ኖሮ ምን እንደምሆን የት እንደምገኝ አላውቅም ነበር። በአሁኑ ወቅት ሁለት ሆነን ተደራጅተን ነው የምንሠራው። በሥራችንም ደስተኞች ነን ፤ የገበያው ነገር ግን የምንፈልገውንና የአቅማችንን ያህል እንድንሠራ አላስቻለንም። ተደራጅተን ወደ ሥራ ከገባንበት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በቂ ገበያ ቢኖረን ኖሮ አሁን ከደረስንበት በእጥፍ ልናድግ እንችል ነበር። የገበያ ትስስር የለም። አንዳንዴ መንግሥት ከሚያዘጋጃቸው የንግድ ትርኢቶች ውጪ የቅዳሜና እሁድ ገበያን ብቻ ነው የምንጠቀመው። እዛ ከውጭ የገቡ ምርቶችም በቀላል ዋጋ ለገበያ ይቀርባሉ። ስለዚህ ውድድሩ ይከብዳል። ሁሌም የምናስበውና የምንጨነቀው ስለምንሠራው ሳይሆን ስለገበያው ነው» በማለት ለዕድገታቸው ትልቁ ተግዳሮት የሆነባቸውን ትገልፃለች። ወደፊት የገበያ ትስስሩ ካለ ለሌሎችም የሥራ ዕድል ለመፍጠር ሀሳብ አላት።
የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር ዶክተር አምባቸው መኮንን ባለፉት ዓመታት በሀገሪቷ በሚገኙ ከ1ሺ 500 በላይ ከተሞች ውስጥ ለሚኖሩ በተለይም ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ዜጎችን በየደረጃው ተጠቃሚ ለማድረግ ሰፊ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ይጠቅሳሉ። ባለፉት ዓመታት በሥራ እድል ፈጠራ አማራጭ የሥራ እድሎችን በማመቻቸት በኩል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ሠርተው ሀብት እንዲያፈሩ ማድረግ ተችሏል። በዚህም የዜጎችን ፍትሀዊ የልማት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችል መሰረት በመጣሉ ዘርፉ ለሀገራዊው የድህነት ማሽቆልቆል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል። በቀጣይም ዘርፉ አድማሱን አስፍቶ ለሥራ የደረሱ ዜጎችን ሁሉ በማቀፍ ለኢንዱስትሪ ሽግግሩ ቁልፍ ሚና እንዲወጣ ለማስቻል የሚሠራው ሥራ የሚቀጥል ይሆናል። ይሄ እንዳለ ሆኖ የገበያ ትስስር አለመኖር የዘርፉ ማነቆ በመሆኑ የተቀመጡት ግቦች እንዳይሳኩ እንቅፋት እየሆነ መሆኑን ይናገራሉ። በመሆኑም እስከ ዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደርስ የገበያ ትስስር መፍጠር፤ እንዲሁም አምራቾች በመጠን፣ በጥራትና በዋጋ ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶችንና አገልግሎቶችን ለገበያው በማቅረብ ብሎም በማስተዋወቅና በመሸጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ይጠበቃል።
ሚኒስትሩ ጨምረው እንዳብራሩት የገበያ ክፍተቱን ለመቀነስ መንግሥት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን መጀመሪያ እስከ ዘንድሮ ሩብ ዓመት ድረስ ከሰባ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የሀገር ውስጥ የገበያ ትስስር ሲሠራ ቆይቷል። አሁንም የዘርፉን ውጤታማነት ለማረጋገጥ ከዚህ በፊት የተጀመሩትን ኢንተርፕራይዞችን ከመንግሥት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ጋር በማስተሳሰርና በመንግሥት ከሚካሄዱ ግዢዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ እና ልዩ ልዩ የማበረታቻ ሥርዓቶችን የማመቻቸት ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል።
የፈጠራ ሥራዎችን በማበረታታትና በዘርፉ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በኢንተርፕራይዞቹ ትስስርና መደጋገፍ እንዲፈቱ የሚያስችል ሥራ መሥራት ቅድሚያ ይሰጠዋል። ክልሎችና ከተሞች በየአካባቢያቸው ኤግዚቢሽንና ባዛሮችን በየወቅቱ በማዘጋጀት ኢንተርፕራ ይዞቹ ምርቶቻቸውን ለማህበረሰቡ በማስተዋወቅና በመሸጥ እንዲጠቀሙ በማድረጉ በኩል የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የፌዴራል የከተሞች የሥራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በከተሞች የሚታየውን ስር የሰደደ የሥራ አጥነትና የድህነት ችግር ለመቀነስ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። ኤጀንሲው በተለያየ ምክንያት መሥራት እየቻሉ ሥራ ለሌላቸው ዜጎች የልማታዊ ሴፍቲኔት ድጋፍ በመስጠት፤ አኗኗራቸውን በማሻሻል የምግብ ዋስትናቸው የተረጋገጠ እንዲሆን የሚሠራቸው ሥራዎች ብዙዎቹን ተጠቃሚ አድርጓል።

 

ራስወርቅ ሙሉጌታ

Published in ኢኮኖሚ

በዓለም ትልቁ ፏፏቴ የቪክቶሪያ መገኛ የሆነችው ደቡብ አፍሪካዊት አገር ዛምቢያ ካለፉት ሳምንታት ወዲህ ትልቅ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ እንደምትገኝ መረጃዎች ሲወጡ ሰንብተዋል። በርካታ ዓለምአቀፍ መገናኛ ብዙሃንም ዛምቢያውያን በሁለት ጽንፍ ያለ አስከፊ ጩኸት ውስጥ እንደሚገኙ በመጠቆም ላይ ናቸው። አንዱ ጩኸታቸው ከሙስና ጋር ተያይዞ የመጣ ጥልቅ ድህነት ሲሆን ሌላኛው የዚሁ ጥልቅ ድህነት ማሳያ የሆነው የኮሌራ ወረርሽኝ ነው። በመጪው 2021 አገሪቱ የምታደርገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫም ሌላ ቀውስ ይዞ መጥቷል። የዛምቢያው ፕሬዚዳንት ኤድጋር ሉንጉ ለሦስተኛ የስልጣን ዘመን ለመወዳደር መዘጋጀታቸውን ተከትሎ በአገሪቱ ውጥረት ፈጥሯል። ሉንጋ እኤአ በ2015 የፕሬዚዳንት ሚካዔል ሳታህ መሞትን ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጡ ሲሆን በ2016 በነበረው ምርጫ አሸናፊ ሆነው ስልጣን መያዝ ችለዋል። እኤአ 2021 በሚደረገው የአገሪቱ ምርጫም እየተዘጋጁ መሆኑ በፓትሪዮቲክ ፍሮንት ፓርቲያቸው ውስጥ መከፋፈል ሊፈጠር ችላል። 

የዛምቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሃሪ ካላባ በማህበራዊ ድረ ገፅ የአገሪቱ የሙስና ሁኔታ እየባሰበት ሄዶ የዜጎች ሁኔታ ያሳስበኛል ብለው ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን አጃንስ ፍራንስ ዘግቦታል። ገዢው ፓርቲ ፓትሪዮቲክ ፍሮንት ጉዳዩን በመጀመሪያም አስተባብሎ የነበረ ቢሆንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ግን ማረጋገጫ ሰጥተውታል። ካላባ በ2014 ወደ ስልጣን የመጡ ሲሆን በዛምቢያ በ2021 በሚካሄደው ምርጫ ሉንጋን ይተካሉ የሚል እምነት ተጥሎባቸው የነበረ ቢሆንም ሉንጋ ህገ መንግስቱን ጥሰው እወዳደራለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ስራቸውን ለቀዋል።
እውቁ የዛምቢያ ጋዜጣ ሉሳካ ታይምስ በገዢው ፓርቲ ውስጥ ባለው ውጥረት ፕሬዚዳንቱ በስልጣን ላይ እንዲቀጥሉ ወይም በህገ መንግስቱ መሰረት የስልጣን ዘመናቸው እንዲያበቃ በሚፈልጉ መካከል ውዝግብ እንደተፈጠረ ፅፏል።
በዚህም ከሳምንት በፊት ፕሬዚዳንቱ የናሽናል ዴቭሎፕመንት ፕላኒንግ ሚኒስትሩን ሉኪ ሙሊሳን እንዲሁም ባለፈው ህዳር የመረጃ ሚኒስትሩን ኪስማ ካምቡዊሊን «ከእኔ ጎን አይደላችሁም» በማለት ከስልጣን አንስተዋል። ይህ አካሄድም ይበልጥ ፓርቲውን ከፋፍሎ ችግር ላይ ሊጥል እንደሚችልም ስጋት ነግሷል። በቅርቡ በአገሪቱ የተፈፀሙ የሙስና ቅሌቶች ለሚኒስትሮቹ የስራ መልቀቅ ማሳያ ተደርገው ተወስደዋል።
አርባ ሁለት የእሳት ማጥፊያ ተሽከርካሪዎች ለመግዛት ለእያንዳንዱ ተሸከርካሪ አንድ ሚሊዮን ዶላር ወጪ መደረጉ በአገሪቱ በቅርቡ የታየ ትልቅ የሙስና ቅሌት ሲሆን የአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የመንገድ ፕሮጀክት አገሪቱ ለመገንባት ባወጣችው ገንዘብ የተበላም ትልቅ ገንዘብ እንዳለ መረጃዎች ወጥተዋል። ይህም ፕሬዚዳንቱ በቀጣዩ ምርጫ ለመወዳደር ማሰባቸው ከወዲሁ በአገሪቱ ዜጎች ቁጣ እንዲቀሰቀስ አንደኛው ምክንያት ሆኗል።
ሙስና በአገሪቱ በየዓመቱ አራት ነጥብ ሰባት በመቶ እያደገ እንደሚገኝ የአሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ ይጠቁማል። የዚህም ውጤት አገሪቱን ለከፋ ድህነት ዳርጎ ዜጎች ተስፋ እንዲቆርጡ እያስገደዳቸው ይገኛል።
የአገሪቱ ባለስልጣናት የተከሰተውን የኮሌራ በሽታ ማቆም እንደተሳናቸው ከቀናት በፊት የወጡ መረጃዎች አመላክተዋል። የቢቢሲ ዘገባ እንደሚያመለክተው በኮሌራ በሽታ የተነሳ ሃምሳ አንድ ዜጎች ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን ከሁለት ሺ በላይ የሚሆኑት በበሽታው ተጠቅተው የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል።
የዓለም የጤና ድርጅት የድሃ አገራት የጥልቅ ድህነት ማሳያ ነው ብሎ የፈረጀው ኮሌራን ለመቆጣጠር አገሪቱ የፈጣን ምግብ አቅራቢዎችን እስከ መዝጋት አድርሷታል። በርካታ ሬስቶራንቶችም ይሄው የኮሌራ በሽታን የሚያስፋፋው ባክቴሪያ ተገኝቶባቸው እንደተዘጉ የቢቢሲ ዘገባ ያሳያል። የአፍሪካ ምርጡ የዶሮ ምግቦች አቅራቢ የአፍሪካው ኬ ኤፍ ሲ እየተባለ የሚጠራው ሃንግሪ ላይን እገዳው አርፎበታል።ዛምቢያ በዚሁ በኮሌራ ምክንያት ኢንቨስትመንት እየራቃት መምጣቱም ታውቋል።
የታንዛኒያው ፕሬዚዳንት ጆን ፖምቢ ማጉፉሊ ለአገሪቱ የስደተኞች ቢሮ ሃላፊ የዛምቢያ ዜጎች ወደ ታንዛኒያ እንዳይገቡ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ለዚህም «ከአስራ አምስት ሚሊዮን ህዝብ በላይ በሌላት ዛምቢያ ኮሌራ ይህን ያህል ጉዳት ካደረሰ ስልሳ ስምንት ሚሊዮን ህዝብ ባላት ታንዛኒያ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ማሰብ ነው» ሲሉ ማጉፉሊ ምክንያታቸውን ተናግረዋል።
የሙካላ ዛፍ ንግድ በህገ ወጥ መንገድ ለውጭ ገበያ እየቀረበ አገሪቱን እየጎዳ እንዳለም ተነግሯል። የዛምቢያ የመሬትና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስትሯ ጂያን ኬፓትም አገሪቱ ከዚህ ንግድ የምታገኘው አንዳች ገንዘብ እንደሌለ ገልፀዋል።
ስልሳ አራት በመቶ የአገሪቱ ዜጎች ከአንድ የአሜሪካን ዶላር በታች ገቢ ያገኛሉ። አስራ አራት በመቶ የአገሪቱ ዜጎችም የኤች አይቪ ኤድስ ተጠቂ ናቸው። አርባ በመቶ ያህሉ ዜጎችም የሚጠጡት ንፁህ ውሃ የለም። ዘጠና በመቶ የሚሆኑ በገጠራማ ዛምቢያ የሚኖሩ ሴቶች ትምህርት ቤት ደጃፍ ደርሰው አያውቁም። ይህ ሁሉ ችግር በአገሪቱ ጫንቃ ላይ ወድቆ ግን ባለ ስልጣኖቿ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ ኪሷን በማውለቅ ላይ ተጠምደው እንደሚታዩ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ።
ዛምቢያ አሁን ላይ ለገጠማት የጤና እክል ብልሹ አሰራር ምላሽ እንዳትሰጥ እጇን አሳጥሮታል። የአገሪቱ ዋነኛ የፖለቲካ ተቃዋሚ ፓርቲ ፓትሪዮት ፎር ኢኮኖሚክ ፕሮግረስ(ፒፒ) መሪ ሲን ኢኖክ ቲምቦ «አገሪቱን ፕሬዚዳንቱ ሊንጎ ወደ ጨለማ እያወረዷት ይገኛሉ» በማለት ተቋውሟቸውን አሰምተዋል። ሉንጉ ግን ትችቶችን በዝምታ አልፈው ለቀጣዩ ምርጫ መንገዶችን እየጠረጉ ይመስላል። የአገሪቱ ዜጎች ግን በኮሌራ ስጋትና ሙስና ባመጣው ጥልቅ ድህነት መካከል ሆነው በሁለት ጽንፍ ያለ አስከፊ ጩኸት እያሰሙ ይገኛሉ።
የበርካታ የቱሪስት መስህቦች ባለቤት የሆነችው ዛምቢያ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በጥልቅ ድህነት ከመኖሯ ባሻገር የዜጎቿ ገቢም በእጅጉ እያሽቆለቆለ ይገኛል። በዚህም ስልሳ አራት በመቶ የሚሆነው ህዝቧ ከድህነት ጠለል በታች ለመኖር ተገዷል። ይህ ቁጥር ወደ ገጠራማው የአገሪቱ ክፍል ሲወርድም ሰማንያ በመቶ ያህሉ ምግብና ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለመሙላት እንዳልቻለ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ቦጋለ አበበ

Published in ዓለም አቀፍ
Saturday, 13 January 2018 19:45

ጣት ቀሳሪዎች

ሀገራችን ውስጥ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን ለሚገኙበት የተዳከመ ሁኔታ ተጠያቂው ገዥው ፓርቲ መሆኑን ሲገልፁ ይሰማል። በተለይም ቅንጅት፣ ሰማያዊና ኢዴፓን የመሳሰሉ ፓርቲዎች ለመዳከማቸው ምክንያት ኢህአዴግ መሆኑን ይናገራሉ። እርግጥ ይህን ጉዳይ በስፋት ለማተት የፓርቲዎቹን ባህሪ፣ የጥምረታቸውን ምክንያትና ያላቸውን የፖለቲካ መስመር ጠንቅቆ ማወቅ ይገባል። በእኔ እምነት በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ተዳክመናል የሚሉ ከሆነ ለመዳከማቸው ምክንያት ገዥው ፓርቲ የሚሆን አይመስለኝም።
እንደ እውነቱ ከሆነ የአንድ ፓርቲ ጥንካሬም ይሁን ድክመት የሚለካው በመስመሩ ጥራት፣ በአባላቱ ጥንካሬና ዲሲፕሊን እንዲሁም የዓላማ ቁርጠኝነት ሆኖ ሳለ፤ ጉዳዩን ወደ ገዥው ፓርቲና መንግሥት ለማላከክ መሞከር ተገቢም ትክክልም አይመስለኝም። እነዚህ ፓርቲዎች በተለያዩ ወቅቶች በ«እሳትና ጭድ» ተምሳሌትነት የሚቀርቡ፣ የሚቧደኑበት ዓላማ በደፈናዊ ጥላቻ የሚመራ፣ በ«ጠላቴ ጠላት…» ቁርኝት የታጀለ፣ ትክክል ያልሆነና ይህ ነው የሚባል የጠራ የፖለቲካ መስመር የሌላቸው ናቸው።
የፓርቲዎቹ ድርሳነ ታሪክ እንደሚያወሳው፤ ተጣማሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በፖለቲካም ይሁን በአመለካከት ምንም ዓይነት ግንኙነት ከሌላቸው ፓርቲዎች ጋር የመዋሃድና አፍታም ሳይቆዩ ደግሞ «እየተቦጫጨቁ» የመለያየት ባህል ያላቸው ናቸው።
እርግጥ ይህን ማንነታቸውን ባለፉት አምስት ሀገራዊ ምርጫዎች ተግባሮቻቸው እንድንገነዘብ ማድረጋቸውን ራሳቸው ባይክዱትም ቅሉ፤ ድክመታቸውን በገዥው ፓርቲና በመንግሥት ላይ ለማላከክ መሞከራቸው ግን «የእናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ» በማለት የራስን ችግር ለመሸፋፈን የሚደረግ አስገራሚ ዲስኩር ይመስለኛል።
«የአብዬን ወደ እምዬ» በማላከክ ጣት የመቀሰር ፖለቲካን ሲያራምዱ እንደነበር ያለፈው ታሪካቸው አፍ አውጥቶ ይናገራል። ፓርቲዎቹ ወትሮም ቢሆን የአቤቱታን ሙግት እያጨዱ መከመር ሥራቸው ነው። ቀደም ባሉት ጊዜያት «እኛ ተፎካካሪ ነን» በማለት ስለ ፖለቲካ ምህዳርና ስለ ምርጫ እንዳላወሩ፤ ዛሬ ደግሞ ለመዳከማችን ምክንያቱ ገዥው ፓርቲና ኢህአዴግ ነው እያሉን ነው።
በእኔ እምነት ሀገሬ እንደ አለመታደል ሆኖ የፖለቲካ ጨዋነት ያለው፣ የተሟላ ሥነ ምግባርና ፕሮግራምን የተላበሰ፣ የጠራ ድርጅታዊ መስመር ኖሮት ህዝብን በአጀንዳው ሊያሳምን የሚችል ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲ አልታደለችም።ሃቁን እንነጋገር ከተባለ የተቃዋሚ ፓርቲዎቻችን ቁመና፣ ታሪክና ሥነ ምግባር ስስ ነው።
ለተወዳዳሪነትም በአቅመ እንደራሴነቱም ያልበቁ ምናልባትም በዚህ ጣት ቅሰራ ፖለቲከኝነታቸው ወደፊትም ለመብቃትና ተመራጭ ሆኖ ለመገኘት ዝግጁነትም ያላቸው አይመስለኝም። ጊዜያቸውን ‘ለእኔ መዳከም ተጠያቂው እገሌ ነው’ ከማለት በስተቀር ራሳቸውን ወደ ውስጥ የመመልከት ባህል የላቸውም። ነገ የተሻለ ተቀናቃኝ ሆነን ለመገኘት ራሳችንን በምን መልኩ ማጠናከር ይኖርብናል ብለው ሲጠይቁና ሲመካከሩ ሰምቼ አላውቅም። ከዚህ ይልቅ በሌላው ላይ ጣት መቀሰር የሚቀናቸው ናቸው።
አሁንም በእኔ እምነት ኢህአዴግ ነፍስ ያወቀ፣ የደረጀና ባለ ራዕይ ድርጅት ነው። እናም ከኢህአዴግ ጋር ራስን አወዳድሮ ሽንፈትን አምኖ መቀበል አግባብነት ያለው አንድ ነገር ነው። አግባብነት የሌለውና የሚያስገምተው ግን አቅምን ባለመገንዘብ ‘የችግራችን ሁሉ ምንጭ ኢህአዴግ ነው’ የሚል ጣት ቅሰራ ነው።
ኢህአዴግን ጨምሮ የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የተውሸለሸለ የፖለቲካ ፕሮግራም ይዞ ሚዛናዊው ህዝብ ፊት መቅረብ አይችልም። የጠራ፣ የህዝብን ቀልብና ፍላጎት የሚማርክ እንዲሁም ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መስመር ሊኖረው ግድ ይላል። አሊያ ግን ህዝቡ እንኳንስ በካርዱ ውክልና ሊሰጠው ቀርቶ የመራጮች ሁሉ ምራጭ እንደሚያደርግ ባለፉት ምርጫዎች በገሃድ አሳይቷል።
ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰበብ አስባቡ ጣታቸውን ወደ ገዥው ፓርቲና ወደ መንግሥት የሚቀስሩት ዜጎችን መማረክ የሚችልና የኢህአዴግ ፕሮግራሞች የሚያስንቁ የፖለቲካ ማኒፌስቶዎች ስለሌሏቸው ይህን እውነታ ለመሸፋፈን ካላቸው ፍላጎት በመነሳት መሆኑን ማንም የሚስተው እውነታ አይደለም። በእኔ እምነት ተቃዋሚ ፓርቲዎች አውርቶ አደሮች እንጂ ባለፉት ዓመታት ህዝብ ዓይን ውስጥ የሚገባ መስመርን አልተከተሉም።
መድረክን የመሳሰሉ ፓርቲዎች በውጭ ኃይሎች የሚመራ ፖለቲካን እዚህ ሀገር ውስጥ የሚያልሙ ናቸው። እንዲያውም በተለያዩ ወቅቶች የአክራሪ ኒዮ ሊበራል ኃይሎች «ዓይንና ጆሮ» ሆነው ሲሰሩ ታዝቤያቸዋለሁ። ይህ ግን ሁሉንም ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የሚመለከት አይደለም። እዚህ ላይ በሀገራዊ መንፈስና በሀገር ተጠቃሚነት እሳቤ የሚንቀሳቀሱ በስነ ምግባር የታነፁ ጨዋ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሃቅ ለመደፍጠጥ አልሻም።
እነ መድረክና ሰማያዊ ግን ለእኔ “እነ አያ ጉዶ” ናቸው። ትናንት ለእነ “ሂዮማን ራይትስ ዎች” ተላላኪ ሆነው የቀለም አብዮት አቀጣጣይ፣ የእነ ቢቢሲ ናይት የውሸት ምስክሮች፣ በውጭ ሃይሎች ግፊት ቤተ መንግስት ገቢዎች ሆነው ራሳቸውን የሾሙ ነበሩ።
የህዝቡን ፍትሐዊ ድምፅ ከመጤፍ ባለመቁጠር ስልጣንን ከምርጫ ኮሮጆ ሳይሆን ከቀለም አብዮት አንጋሾች ለማግኘት ደፋ ቀና ይሉ እንደነበር አስታውሳለሁ። ይህ አሳፋሪ ማንነት የታሪካቸው አካል ሆኖም እንደ ጥላ እንደሚከተላቸው የተገነዘቡት አይመስሉም።
እናም “እነ አያ ጉዶ” ዛሬ ‘እኛ ያልባረክነው ወይም የሌለንበት ድርድር ዋጋ የለውም’ ብለው አሊያም እንዲሉ “በአንጋሾቻቸው” ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው በሰጥቶ መቀበልና በፍፁም ሀገራዊ ጥቅም እየተካሄደ ያለው ድርድር ቁብ አልሰጣቸውም። ይህም ምን ያህል ለሀገራቸው ፖለቲካ ምህዳር መስፋት ደንታ ቢሶች እንደሆኑ የሚያሳይ ነው።
እናም ጠቧል የሚሉት የፖለቲካ ምህዳር ካለ፣ ራሳቸው ውስጥ ገብተው በዴሞክራሲያዊ መንገድ ታግለው ሃሳባቸውን ማቅረብ ሲችሉ ውጭ ሆነው ለመዳከማችን ምክንያቱ ገዥው ፓርቲና መንግስት ናቸው ቢሉ የሚያገኙት አንዳች ትርፍ ሊኖር አይችልም። ሰላማዊ ድርድርን ረግጦ በመውጣት የሚገኝ ዴሞክራሲን የማጎልበት ሂደት ምን ዓይነት እንደሆነ የሚያውቁት እነርሱ ብቻ ይመስሉኛል።
ስለ ተቃዋሚዎቹ ድክመትና ጣት ቀሳሪነት ሳወሳ ገዥው ፓርቲ ምንም ዓይነት ችግር የለበትም እያልኩ አይደለም። ሌላው ቀርቶ ሰሞኑን በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ደረጃ ለ17 ቀናት ባካሄደው ግምገማ ራሱን በሚገባ አይቷል። ችግሮቼ ብሎ ያነሳቸውን ጉዳዩች ከ‘ሀ’ እስከ ‘ፐ’ ዘርዝሮ ህዝቡን ይቅርታ ጠይቋል። የችግሮቹ አልፋና ኦሜጋ ራሱን አደርጎ ኮንኗል። በእኔ እምነት ይህ ራስን መሄስ ትልቅነት ነው። የችግሮች ምንጭ እኔ እንጂ ሌላ አካል አይደለም ብሎ ማመን ብስለት ነው። ጣትን በሌላ ላይ ከመቀሰር የሚመጣ ውጤት አለመኖሩን መገንዘብ አዋቂነት ነው። እናም ከዚህ የኢህአዴግ መንገድ መማር ተገቢ ይመስለኛል። ራስን ወደ ውስጥ አይቶ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት መሞከር እንጂ የጣት ቅሰራ ፖለቲካ ለማንም የማይጠቅም የሽሽት መንገድ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ስለሆነም ተቃዋሚ ፓርቲዎች “ኢህአዴግ አዳከመን” ከማለት ለምን ተዳከምን ብለው ራሳቸውን ቢፈትሹ ምላሹ ራሱ እጁን አውጥቶ “እዚህ ነኝ” የሚላቸው መሆኑን ማወቅ ያለባቸው ይመስለኛል።
ያም ሆኖ ግን በእኔ እምነት እነርሱ እንደሚሉት ተቃዋሚዎቹን ኢህአዴግ አዳክሟቸው ከሆነ፤ ይህ ክስተት የእነርሱን ተሸናፊነትና የኢህአዴግን ጥንካሬ የሚያሳይ ይመስለኛል። ይህ ማለት ተቃዋሚዎቹ ሲጀመር ለመዳከም የተዘጋጁ መሆናቸውን ያመላክታል። ለመዳከም ዝግጁ የሆነ አካል ደግሞ ውስጣዊ ጥንካሬ የሌለው፣ ለውሸት የተሰባሰበ፣ አባላቱ የጋራ ግብና ራዕይ የሌላቸው ከመሆን የሚዘሉ አይደሉም። እናም እርግጥም እነርሱ እንደሚሉት ተቃዋሚዎቹን ኢህአዴግ አዳክሟቸው ከሆነ ማፈር ያለባቸው በራሳቸው ውስጠ ፓርቲ ጥንካሬና አንድነት እጦት እንጂ፣ ችግራቸውን ለመሸፋፈን በሌላው ላይ ጣት መቀሰርን አይመስለኝም።
ዳሩ ግን እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ገዥው ፓርቲም ይሁን መንግስት ዴሞክራሲን እንደ ህልውና የያዙ ናቸው። የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱን ለማጠናከርና በጣት የሚቆጠር ደጋፊ ያላቸውን ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሀገራቸው ጉዳይ ቢሳተፉ አነስተኛም ቢሆን የህዝቡን ድምፅ ለማክበር ያስችላል ብለው የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እስከ ድርድር የዘለቀ ስራዎችን እያከናወኑ ነው። ይህን የሚያደርጉት ድርጅትና መንግስት የረባ የፖለቲካ መስመር የሌላቸውን ተቃዋሚዎችን ያዳክማሉ ብሎ ለማሰብ እጅግ ይከብዳል። ውሃ የማይቋጥርና ሚዛን የማይደፋ አስተሳሰብም ነው።
እናም ጣት ቀሳሪ ፖለቲከኞች “አመልካች ጣትን ወደ ሌላው ስተቀስር ቀሪዎቹ ወዳንተ ያመለክታሉ” የሚለውን ብሂል ሊዘነጉት አይገባም ባይ ነኝ። የተቃውሞ ፖለቲካ ግብ መነሻውን ማድረግ ያለበት ራስን ብቁ ከማድረግ እንጂ፤ ገና ከወዲሁ በፈጠራ ድርሰት ‘እገሌ አዳከመኝ’ እያሉ በመልፈስፈስ አይደለም።
የፖለቲካ ስራ እንደ ሽሮ ፈሰስ አሁን ተዘጋጅቶ አሁን የሚደርስ አይደለም። ጊዜን ይጠይቃል። የትግሉም ሂደት አልጋ በአልጋ አይደለም። አባጣ ጎባጣ የበዛበት፣ ረጅም አቀበትን መውጣትና ቁልቁለትን መውረድ እንዲሁም ሰው ወሳጅ ፈረሰኛ ውሃን የያዘ ወንዝ በድፍረት መሻገር የግድ ይላል። የተቃውሞው ጎራ እነዚህን ሂደቶች ሃሞተ ኮስታራ ሆኖ ማለፍ አለበት። የፖለቲካ ስራ ዳር ቆሞ የጣት ቅሰራ ፖለቲካ ሐሜት አራማጅነት የሚመራ አይደለም። ስንክሳሮችንና አሜኬላዎችን እየተጋፈጡ ራስን በማብቃትና ህዝብን የሚያማልል ፕሮግራም ቀርፆ ወደሚፈለገው ግብ መድረስ ይቻላል።
የተቃውሞ ጎራው ይህን ማድረግ ከቻለ ሁለት ነገር ሊያተርፍ ይችላል ብዬ አስባለሁ። አንደኛው፤ ከተራ ውንጀላ ወጥቶ ራሱን በመፈተሽ የጠራ መስመር ኖሮት የህዝቡን ቀልብ ሊያሸፍት መቻል ነው። ሁለተኛው ደግሞ፤ ሀገሪቱ እያከናወነች ባለችው የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በሚደረገው ጥረት ላይ የራሱን አሻራ ሊያሳርፍ ይችላል። ይህን ማድረግ ከተሳነው ግን ነገም ሆነ ከነገ በስቲያ ከፈጠራ ውንጀላ ፖለቲካና ከጣት ቀሳሪ ፖለቲከኞች የሚላቀቅ አይመስለኝም።

ዘአማን በላይ

Published in አጀንዳ


ለኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ ለአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ፣ ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች ማረፊያና መሰብሰቢያ ናት-አዲስ አበባ። በ1878ዓ.ም በአጼ ምኒልክ ዘመን እንደተቋቋመችና በእቴጌ ጣይቱ ስም እንደወጣላት የሚነገርላት ይህቺ ከተማ አሁንም ስሟ ያማረ ይሁን እንጂ ውበትና ጽዳቷ በስሟ ልክ አልሆነም።በጣት ከሚቆጠሩ አካባቢዎች በቀር አብዛኞቹ ጎዳናዎቿ እጅን በአፍንጫ የሚያስጭኑ፤ለዓይንና ለመንፈስ ደስ የማያሰኙ ናቸው።በየመንገዶች ዳር ዳር፣በፍሳሽ ማስወገጃዎች፣በወንዞች መውረጃ፣በየጥጋጥጉ አፍንጫን የሚተነፍገው ሽታና እንደ ጤፍ በጆንያ የሚታየው የቆሻሻ ክምር ከተማዋን እንደስሟ ያማረች እንዳትሆን አድርገዋታል።
የከተማው አስተዳደር ይህንን ችግር ለመቅረፍ በተለያየ ጊዜ የጽዳት ዘመቻዎችን በማድረግ፣ በግለሰቦች ተነሳሽነትና በሌላው ነዋሪ ተሳትፎ ከተማችንን ንፁህ እናደርጋለን በሚል እንቅስቃሴ እንደነበር የሚታወስ ነው።በዚህም ለውጥ የታየበት፣ የቆሻሻ መጣያ የሆኑ ስፍራዎች ወደ ማረፊያና መዝናኛነት የተለወጡበት ሁኔታ አለ።ሆኖም ግን ይሄ በተለያየ ጊዜ እንደ ወረት የሚነሳው ዘመቻ ወቅታዊ ከመሆን የዘለለ አይደለም።በውጤቱም መሰረታዊ ለውጥን አላመጣም።ምክንያቱም ለወረት የአንድ ሰሞን ሆይ ሆይታ ሆኖ ዘላቂ ሳይሆን ይቀራል።የተጸዳውም አካባቢ መልሶ ወደነበረበት ይገባል።
በከተማዋ በአሁኑ ወቅት በመኖሪያ አካባቢዎች ተደራጅተው በጽዳት ስራው በቋሚነት የሚሠሩ 560 የጽዳት ማኅበራት፣33 የግል ጽዳት ድርጅቶች እንዲሁም በመንግስት የተቀጠሩ ከአምስት ሺ በላይ መንገድ የሚያፀዱ ሠራተኞች አሉ።ሆኖም ግን ከተማዋ ካላት የቆዳ ስፋት እንዲሁም ነዋሪው አካባቢውን ብሎም ከተማውን ለማጽዳት ካለው የአስተሳሰብ ችግር አንፃር የከተማዋን ፅዳት ከስሟ በሚመጥን ደረጃ ጽዱና ውብ ማድረግ አልተቻለም።ይህም በአይን አይቶ ከመፀየፍም በላይ ለተለያየ የጤና ችግር የሚዳርግ ሆኗል።
በመከላከል ላይ የተመሰረተ የጤና ፖሊሲን ከሚከተል አገርና ከተማ ለጤና ችግር መቀስቀሻ የሚሆን ቆሻሻና መጥፎ ጠረን ይዞ መጓዝ ይጣረሳል። በትምህርት፣ በስልጣኔና ቴክኖሎጂ ወደፊት እየገሰገሰች ከምትገኝ ከተማም ይሄ ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ አይደለም። ሆኖም ግን ለረጅም ዓመታት ከመጣንበት በቆሻሻ ላይ ካለን የአስተሳሰብ ችግር አንፃር አሁንም ችግሩን ለመቅረፍ ያለው ተነሳሽነት በአነስተኛ ደረጃ ላይ ነው።
በመሆኑም የከተማው አስተዳደር ከህዳር 30 ቀን 2010 ጀምሮ «እኔ አካባቢዬን አፀዳለሁ እናንተስ» በሚል ወር በገባ የመጨረሻው ቅዳሜ ወርሀዊ ዘመቻ ቀን በሚል ሰይሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አስጀማሪነት የጽዳት ዘመቻ ተካሂዷል።ለሁለተኛ ጊዜም እንዲሁ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች በዋና ጎዳናዎች ላይ ወጥተው ይሄንኑ ቃላቸውን በተግባር አሳይተዋል። ሆኖም ግን ይሄ ዘመቻ የአመራሩ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም የከተማዋ ነዋሪዎች መሆን አለበት።በሁለት ዙር የታዘብነው ግን በወረዳ ደረጃ ማስተባበሩ ተሰርቶ በወጣቶች፣ በሴቶች እና በሌላውም የከተማው ነዋሪ የነበረው ተሳትፎ እጅግ አነስተኛ እንደነበር ነው።በመሆኑም ከተማዋን ንጹህና ጽዱ የማድረጉ ዘመቻ ከአመራሩ ወደታች ወርዶ የነዋሪው እንዲሆን መሰራት አለበት።
በዚህ ዙሪያ የመገናኛ ብዙሀን ያደረጉት ተሳትፎና ቅስቀሳም አነስተኛ ነው።በመሆኑም ከተማዋን ለማጽዳት መነሳሳቱ የሁሉም የከተማው ነዋሪ እንዲሆን በወረዳዎች፣ በአደረጃጀቶች በኩል ሰፊ ቅስቀሳ ማድረግ ይገባል።ከፍተኛ ባለስልጣናት ካለባቸው የስራ ኃላፊነትና ብዛት አንፃር ለዘመቻው ቀዳሚ ተባባሪ በመሆን በግንባር ቀደምትነት መነሳሳታቸው የሚያስመሰግናቸው ነው።ሆኖም ግን ሁሉንም ስራና ኃላፊነት እነሱ ላይ መጣል ደግሞ ተገቢ አይሆንም።ዘመቻውም ለውጥ የሚያመጣ ሳይሆን ከዚህ ቀደም እንዳየነው የወረት መሆኑ አይቀርም።ስለዚህ የአካባቢን ቆሻሻ ማጽዳት፣ከየቤታችን የሚወጣውን ቆሻሻ በአግባቡ ለይቶ ማስወገድና በወርሀዊው የጽዳት ዘመቻ ላይ መሳተፍ ያሰብነውን ለውጥ እንደሚያመጣ በመረዳት ተሳታፊ መሆን ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል።አቅም ያለው በጉልበቱ አቅም የሌለውና ገንዘብ ያለው በገንዘቡ ቢሳተፍ ፅዱ ከተማ እያልን እንደምንመኛቸው ከተሞች ለመሆን እንችላለን።ነገር ግን አሁን እንደምናየው በባለስልጣን ክንድ ብቻ ከተማዋን ባሰብነው ደረጃ እናፀዳለን ብሎ ማሰብ « ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክም ...» እንደማለት ይቆጠራል።ስለዚህ ከተማዋን የማጽዳቱ ወርሀዊ ዘመቻ ከከፍተኛ አመራሩ ወደ ታች ይውረድ!

 

Published in ርዕሰ አንቀፅ

አዲስ አበባ፦ በጥቃቅንና አነስተኛ ደራጅተው በተለያየ የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶች ውጤታማ መሆናቸውን አስታወቁ።በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ ወጣቶች በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት በተለያዩ የሥራ መስኮች በመሰማራትና ጠንክረው በመሥራታቸው ውጤታማ ሆነዋል። ከራሳቸውም አልፈው ለሌሎችም የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል።በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሉባባ ሲራጅ እንዳሉት በ2006 ዓ.ም

በ2ሺ 500 ብር የልብስ ስፌት ሥራ ጀምረው በአሁኑ ወቅት የ100 ሺ ብር ካፒታል ባለቤት ለመሆን በቅተዋል። ወይዘሮ ሉባባ በአሁኑ ወቅት በኑሯቸውም ሆነ በሥራቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው ወደሥራው ከመግባታቸው በፊት ከነበራቸው ህይወት የተሻለ እየኖሩና ከራሳቸውም አልፎ ሁለት ሠራተኞችን ቀጥረው ማስተዳደር መቻላቸውን ተናግረዋል።
በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ወይዘሪት ማንለኝ አምዲሳ ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት በጥቃቅንና አነስተኛ በመደራጀት ራሷን በኑሮ ለመለወጥ መቻሏን ትገልጻለች። ወይዘሪት ማንለኝ እንደምትለው ወደዚህ ሥራ መግባቷ የራሴ የምትለው ሥራ እንዲኖራትና በየወሩም ቁጠባ እንድታስቀምጥ አስችሏታል። የምትሠራው የቆዳ ምርቶች ዝግጅትም በባህሪው በተናጥል የሚሠራ ባለመሆኑ በሥሯ ከምታሠራቸው በተጨማሪ ለተለያዩ ግለሰቦች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንዳስቻላት ተናግራለች።
የባህል አልባሳት አምራች የሆነችው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሪት በላይነሽ ታረቀኝ በበኩሏ በሦስት ሺ ብር ካፒታል ሥራዋን ከጀመረች አንድ ዓመት እንደሆናትና በዚህ ጊዜ ውስጥ የሚያበረታታ ለውጥ ማየቷን ገልጻለች። በተለይም የምትሠራቸው ሥራዎች የራሷን ዲዛይን ተጠቅማ መሆኑ የፈጠራ ችሎታዋን እንድታወጣ አስችሏታል። በሥሯም ለአምስት ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር አስችሏታል።
የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር ዶክተር አምባቸው መኮንን ባለፉት ዓመታት በሥራ ዕድል ፈጠራ አማራጭ የሥራ ዕድሎችን በማመቻቸት በኩል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ሠርተው ሀብት እንዲያፈሩ ማድረግ መቻሉን ይናገራሉ። በዚህም የዜጎችን ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችል መሰረት በመጣሉ ዘርፉ ለሀገራዊው የድህነት ማሽቆልቆል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
በቀጣይም ዘርፉ አድማሱን አስፍቶ ለሥራ የደረሱ ዜጎችን ሁሉ በማቀፍ ለኢንዱስትሪ ሽግግሩ ቁልፍ ሚና እንዲወጣ ለማስቻል የሚሠራው ሥራ ይቀጥላል። የገበያ ትስስር ችግሮችን ለመፍታትም እስከ ዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደርስ የገበያ ትስስር መፍጠር፤ እንዲሁም አምራቾች በመጠን፣ በጥራትና በዋጋ ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶችንና አገልግሎቶችን ለገበያው በማቅረብ፣ በማስተዋወቅና በመሸጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል የሚጠበቅ መሆኑንም አስረድተዋል።

 

ራስወርቅ ሙሉጌታ

 

Published in የሀገር ውስጥ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካሳለፍነው ኅዳር ወር ጀምሮ አዲስ አበባን ከስሟና ዝናዋ ጋር ለማመሳሰል፣ የፅዳት ባህልን ለማዳበር በየወሩ የመጨረሻ ቅዳሜ አካባቢን የማፅዳት ዘመቻ ጀምሯል። በዚህ የፅዳት ዘመቻ ህብረተሰቡ በሙሉ ተሳታፊ መሆን ችሏል ወይ?በቦሌ ክፍለ ከተማ የረር በር አካባቢ ነዋሪ ወይዘሪት አበባ ስዩም በተለይም በየረር በር እና ገርጂ አካባቢ በሚገኝ ወንዝ ላይ ቆሻሻ ይጣል እንደነበር ትጠቅሳለች። አሁን ግን በየአካባቢው በመንቀሳቀስ በየግቢው ያለውን ቆሻሻ የሚያነሱ ወጣቶች በመኖራቸው በየቦታው የሚታየው ቆሻሻ መቀነሱን ትናገራለች።

«አሁንም ግን መንገድ ላይ ተጥሎ የሚታይ ቆሻሻ አለ። ወጣቶቹ ቆሻሻ ከየቤቱ እያነሱ ቢሆንም ቆሻሻውን መንገድ ላይ የሚጥል ደግሞ አለ። ማታ ንጹህ የነበረ መንገድ ማለዳ በፌስታል የተቋጠረ ቆሻሻ ይገኛል» ትላለች።
ወይዘሪት አበባ በከተማዋ የተጀመረው በወር አንድ ቀን በጋራ አካባቢን የማፅዳት እንቅስቃሴ በመገናኛ ብዙሃን የሰማች መሆኗን ጠቅሳለች። ምንም እንኳን በአካባቢዋ በዚህ እንቅስቃሴ ላይ የተሳተፈች አለመሆኗንና ሥራው ስለመሠራቱም መረጃው እንደሌላት ብትጠቅስም በነገሩ ደስተኛ ናት። ይህም በየጊዜው የሚቀጥል ከሆነ የመኖሪያ አካባቢያቸው የበለጠ ንጹሕ እንደሚሆን ነው የምትናገረው።
«ጉሊቶችና የገበያ ማዕከላት አካባቢ የሚታየው ቆሻሻ በአካባቢው ሰው የለም የሚያሰኝ ነው። በአካባቢው የሚንቀሳቀሰውም ሳይላመደው አልቀረም። ነገር ግን መልካም የሚሆነው አረንጓዴና ንጹሕ አካባቢን ብንወድና ብንለምድ ነው» ያሉን አቶ አህመድ ዓሊ ናቸው።
እንደእርሳቸው ገለጻ የቆሻሻ መጣያዎች በየቦታው በስርዓት አለመኖራቸው አንድ ትልቅ ችግር ነው። ከዚያ በተጓዳኝ ግን የከተማዋ ነዋሪ ለአካባቢው ግድ የለሽ መሆን እንደሚታይበት የተጠቀመበትን ነገር ሁሉ ከራሱ መራቁን እንጂ የት እንደጣለ የማያስተውሉ በርካታ መሆናቸውን ከትዝብታቸው ያስረዳሉ። በተለይም ባለመኪናዎች ሶፍት፣ የውሃ ፕላስቲክ፣ ወረቀትና መሰል ዕቃዎችን ከመኪና በመስኮት በኩል ሲጥሉ የሚያዩ መሆናቸውን ይናገራሉ።
የተጀመረው አካባቢን በጋራ የማፅዳት ዘመቻ ጥሩ ቢሆንም ሁሉም የከተማው ነዋሪ ተሳትፎ እየሠራ እንዳልሆነ መታዘባቸውን ጠቅሰዋል። እሳቸውም ሆኑ ሌሎች በዚህ ሥራ ያልተሰማሩት አካባቢውን የሚያስተባብር የመንግሥት አካልም ሆነ ሌላ ባለመኖሩ ነው። ለአካባቢው ውበትና ንጽሕናን የማይፈልግ ሰው ስለማይኖር በወር አንድ ቀን በሚካሄደው ዘመቻ ላይ ወጣቶችና ሴቶች እንዲሳተፉ ቢደረግ መልካም ነው። አሁን በከፍተኛ አመራሩ ብቻ የሚደረገው የፅዳት ዘመቻ ለውጥ ያመጣል ብሎ መጠበቅ አይገባም የሚል ሃሳብ አላቸው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ቆንጂት ደበላ እንዳሉት በመኖሪያ አካባቢዎች ተደራጅተው የሚሠሩ አስር አባላት ያሏቸው 560 የፅዳት ማኅበራት፣ ከየተቋማቱ የሚሰበስቡ 33 የግል ፅዳት ድርጅቶች እንዲሁም መንገዶችን የሚያፀዱ በመንግሥት የተቀጠሩ ከ5ሺ በላይ ሠራተኞች ቢኖሩም የከተማዋን ፅዳት ከስሟ በሚመጥን ደረጃ አላደረሳትም።
በመሆኑም የጎረቤት አገራትን በተለይም የሩዋንዳዋ ኪጋሊ ከተማ ልምድ በመውሰድ የፅዳት ሥራው መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ህብረተሰብን በማሳተፍ መጀመሩን ተናግረዋል። በዚህም የአዲስ አበባን ነዋሪ በንቅናቄ መልክ ማሳተፍና ይህንንም ቋሚ ለማድረግ ተወስኗል።
በግንዛቤ ማስጨበጫ በወረዳዎች ከ70 ሺ በላይ ሰዎችን በማወያየት፣ በትምህርት ቤቶች፣ በወረዳ፣ መገናኛ ብዙሃን፣ ከኪነጥበብ ባለሙያዎችና መሰል ጋር እንዲሁ ተመሳሳይ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል። ከሁሉም የተገኘው ምላሽ «አስተባብሩን እንጂ እኛ ንፁህና አረንጓዴ አካባቢ እንፈልጋለን» የሚል ሃሳብ ነው። ይሄና የሌሎች አገራት ልምድ ተዳምሮ በየወሩ የመጨረሻው ቅዳሜ የፅዳት ቀን እንዲሆንና ሁሉም አካባቢውን እንዲያፀዳ ተደርጓል።
የመጀመሪያው የፅዳት ቀን ኅዳር 30 ቀን በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዲሁም በከፍተኛ አመራሮችና ሚኒስትሮች ሲጀመር 250ሺ፣በሁለተኛው ዙር ታህሳስ ወር መጨረሻ 470 ሺ የከተማዋ ነዋሪዎች ተሳታፊ መሆናቸውን ገልጸዋል።
«በዚህ በአንድ ጊዜ ይለወጣል ማለት አይደለም። ሁሉም ክፍለከተማ ተመሳሳይ አፈጻጸም የለውም። በአንድ ጊዜ ሁሉም ጋር ይዳረሳል ብለንም አላቀድንም፥ ባህል እስከሚሆን ድረስ ግን እንሠራለን» ብለዋል። አያይዘውም «እንደዘርፉ ባለድርሻ አካል እኛ ጠንክረን ካልሠራን ሌላው ጋር ለውጥ ማምጣት አንችልምና ከራሳችን መጀመር አለብን ብለን መሥራት አለብን» ብለዋል፥ ምክትል ሥራ አስኪያጇ።

ዜና ሀተታ
ሊድያ ተስፋዬ

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 3

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።