Items filtered by date: Tuesday, 02 January 2018
Tuesday, 02 January 2018 18:41

መካከለኛው ምስራቅ በ2018

ስምንት የምስራቃዊ አውሮፓ አገራት ባለፉት አራት አመታት ብቻ ከአንድ ቢሊዮን ፓውንድ በላይ የሚያወጣ የጦር መሳሪያ ለመካከለኛው ምስራቅ አገራት መሸጣቸው የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከስምንት የምስራቃዊ አውሮፓ አገራት ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገራት ከገቡት በሺህዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ ከባድና ቀላል የጦር መሳሪያዎች መካከል አብዛኞቹ በእርስ በርስ ጦርነት ወደምትታመሰው ሶርያ ደርሰው ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡

 የጦር መሳሪያዎቹን የሸጡት አገራት ቦስኒያ፣ ቡልጋሪያ፣ ክሮሺያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ሞንቴኔግሮ፣ ስሎቫኪያ፣ ሰርቢያና ሮማኒያ ሲሆኑ፤ አገራቱ እ.ኤ.አ ከ2012 አንስቶ ባሉት አመታት በድምሩ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሳሪያ ለሳኡዲ አረቢያ፣ ለዮርዳኖስ፣ ለተባበሩት አረብ ኢሜሬትስና ለቱርክ ሸጠዋል፡፡ የጦር መሳሪያዎቹ በመካከለኛው ምስራቅ አገራት በሚገኙ አክራሪ ቡድኖች በጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ፡፡ 

ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት ያለፉት አመታት ለመካከለኛው ምስራቅ አገራት ምቹ አልነበረም፡፡ በመጪው የፈረንጆች አመትም በዚሁ የሚቀጥል ይመስላል፡፡በአካባቢው የጦርነት አዝማማሚያዎች እየታዩ ቢገኙም ግጭቶችን በሰላምና በድርድር እንዲፈቱም ጫናዎች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ የመጪው የፈረንጆች አዲስ አመት የሰላም ድርድር የሚደረግበት፣ የምርጫና በጦርነት የተጎዱ ከተሞች ግንባታ ይኖራል ተብሎ ተስፋ ቢደረግም  የመን አዲሱን አመት ካለምንም የሰላም ድርድርና አካባቢያዊ ግጭት በነበረችበት ልትቀጥል እንደምትችል አልጀዚራ በድረገፁ ያሰፈረው መረጃ ያሳያል፡፡

የአልጀዚራ ድረገፅ ፀሀፊ ጆ ማርኮን እንደሚለው፤በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ያለው የፖለቲካ ቀውስ ከባድ በመሆኑ በአዲሱ የፈረንጆች አመትም ትኩረት እንደሳቡ ይቀጥላሉ፡፡ በተለይ ደግሞ ሶሪያ፣የእየሩስአሌም ጉዳይ፣ኢራቅ፣ሊቢያ እንዲሁም የአይ.ኤስ ጉዳይ ተጠቃሽ ነው፡፡ጆ ማርኮን በአልጀዚራ ድረገፅ ላይ በመካከለኛው ምስራቅ በ2018 ምን ሊከሰት እንደሚችል ያሰፈረው ፅሁፍ አምስት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡

ሶሪያበአሁን ሰዓት አምስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሶሪያውያን ከአገራቸው ተሰደው በሌሎች አገራት እንደተጠለሉ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን መረጃ ያሳያል፡፡ ስደተኞቹ በጎረቤት አገራት በቱርክ ሶስት ነጥብ አራት ሚሊዮን፣በሊባኖስ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን እና በጆርዳን 650ሺ  ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ እአአ 2017 የተወሰኑ ስደተኞች ወደ አገራቸው እየተመለሱ እንደሚገኙና በአዲሱም የፈረንጆች አመት ስደተኞቹ ወደ አገራቸው የሚገቡበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ዘገባው ይጠቅሳል፡፡ ጆርዳንና ቱርክ ለስደተኞቹ መንቀሳቀሻ ቋሚ ዞኖች ቢሆኑም ስደተኞቹ ወደ አገራቸው እንዲገቡ ጫና እያደረጉ አይደለም፡፡ የሊባኖስ መንግስት ግን በደማስቆ አካባቢ የሶሪያ መንግስት የያዛቸውን አካባቢ ለመቆጣጠር ያሰበ ሲሆን የሶርያ ስደተኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱና የሰላም ውይይቶች እንዲኖሩና አገሪቱ ወደ ነበረችበት እንድትመለስ ያለመ ስራ መሆኑ በአዲሱ አመት ሶርያ ተስፋ እንዳላት ዘገባው ይጠቅሳል፡፡

እየሩሳሌም

ፍልስጤም አሜሪካ ባሳለፍነው ሳምንት የእስራኤል ዋና ከተማ እየሩሳሌም መሆንዋን በተቀበለችበት ወቅት በድጋሚ በአረብ አገራት ፖለቲካ ዋነኛ መነጋገሪያ ርዕስ መሆንዋን ዘገባው ያሳያል፡፡በዚህም ምክንያት እየሩሳሌም በመካከለኛው ምስራቅ አገራት የፖለቲካ ማጠንጠኛ ሆና በአዲሱ አመት ብቅ እንደምትልም ዘገባው አትቷል፡፡ በዚህም ቱርክ ከአሜሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ስትቀንስ ሳውዲና ጆርዳን ደግሞ በጉዳዩ ላይ እየተወያዩ ይገኛሉ፡፡ የአሜሪካን ውሳኔ ተከትሎ በፍልስጤምና በእስራኤል መካከል  የነበረው አለመረጋጋት ቀጥሏል፡፡ አሜሪካ ሳውዲና እስራኤል ከኢራን ጋር ግንኙነት እንዳይኖራቸው የማድረግ ስራ የሚጠበቅባት ሲሆን፣ ሳውዲ በዌስት ባንክ አካባቢ የሚታየውን የመብት ጥሰት ለማስቆም ግፊት እያደረገች ትገኛለች፡፡እአአ 2018 በእየሩስአሌም ጉዳይ አዲስና የቀድሞ የአሜሪካ ወዳጆች የሚታዩበት ሁኔታ እንደሚፈጠርና በሶርያ አካባቢ የነበረው የጦርነት እንቅስቃሴ የሚቀዛቀዝበት ወቅት እንደሚሆን ዘገባው ያትታል፡፡

ሳውዲባልተጠበቀ ሁኔታ እአአ 2017 ላይ እየገነነ የመጣው የሳውዲው ንጉስ መሀመድ ቢን ሰላም በአዲሱ አመትም ገናናነቱ እንደሚቀጥል ዘገባው ጠቅሷል፡፡ ንጉሱ ወደ ስልጣን ለመምጣት እንቅስቃሴ የጀመረው እአአ 2015 ላይ ሲሆን በወቅቱ የሳውዲ አልጋ ወራሽ ነበር፡፡ በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ያለው ቀውስ አላማውን በፍጥነት ለማሳካት የረዳው ሲሆን በተጨማሪም በሳውዲ ያለው የውስጥ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማደግ የውጭ ፖሊሲው ላይ ለውጥ እንዲያመጣ አስገዳጅ ሁኔታ ፈጥሮለታል፡፡ የቀድሞ የሳውዲ ንጉስ መሀመድ ቢን ናየፍ በሃይል ከስልጣኑ እንዲለቅ ከተደረገ በኋላ ሳውዲ በኳታር ላይ የተነሳውን ተቃውሞ መምራት ችላለች፡፡ የሳውዲ መኮንኖች እና ነጋዴዎች በህዳር ወር ውስጥ በሪዝ ካርተን ውስጥ ተሰብስበው በነበሩበት ጊዜ የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳአድ ሐሪሪ ወደ ሪያድ ለመሄድ ተገደዋል፡፡ በአዲሱ የፈረንጆች አመትም የሳውዲው ልዑል በሚከተለው የውጭ ፖሊሲ ሳውዲ ከሌሎች አገራት ጋር ያላት ግንኙነት ሊለወጥ እንደሚችል ዘገባው ይጠቅሳል፡፡

ምርጫዎች

በፈረንጆቹ አዲስ አመት በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ አገራት አካባቢ ጦርነት ቆሞ ወደ ሰላምና መረጋጋት በመመለስ ምርጫ እንደሚካሄድ ዘገባው ይገልፃል፡፡ በመጋቢት ወር የግብፅ የፕሬዚዳንት በግንቦት ወር ደግሞ በሊባኖስ የሚካሄዱት የፓርላማ ምርጫዎች አዲስ ነገር እንደማይሆኑ የጠቀሰው ዘገባው፤ በሊቢያና በኢራቅ የሚካሄዱት የፓርላማና የፕሬዚዳንታል ምርጫ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጠበቅ  አስፍሯል፡፡

የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃድር አል አባዲ ስልጣን ከያዙ በኋላ አይ.ኤስን ድል በማድረግና የኩርዲሾች እራሳቸውን ችለው እንዲተዳደሩ ምርጫ እንዲካሄድ በማድረጋቸው ባገኙት ተቀባይነት በምርጫው ሰፊ እድል እንደሚኖራቸው ዘገባው ተናግሯል፡፡በኢራቅ የፀረ ሙስና ዘመቻን በመምራት ምርጫው እንዲከናወን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ የአባዲ በስልጣን መቆየት አሜሪካ በኢራቅ የሚኖራትን ቆይታ የሚያራዝምላት ሲሆን ኢራን በምርጫው ወቅት ያለውን የፖለቲካ ቀውስ በማርገብ የአባዲን አሸናፊነት ልታከብደው እንደምትችል ዘገባው ጠቅሷል፡፡

በሊቢያ በአዲሱ የፈረንጆች አመት ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ምርጫ ሙሉ ለሙሉ በእርግጠኝነት መናገር እንደማይቻል ዘገባው ያሳያል፡፡ ለአገሪቱ ፕሬዚዳንትነት ለሚደረገው ምርጫ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጠባቂና የጦር መሪ ጄነራል ካሊፍ ሀፍተርና የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሙዐመር ጋዳፊ ልጅ ሰይፍ አልኢስላም ለመወዳደር ቀርበዋል፡፡ በአገሪቱ ምርጫውን ለማካሄድ የሚረዳ አደረጃጀትና የፀጥታ ሁኔታዎች ለማምጣት በአገሪቱ የሚገኙት ተቀናቃኞች በጋራ ሊሰሩ እንደሚችሉ ዘገባው አስፍሯል፡፡

የሊቢያ የምርጫ ባስልጣናት ሰሞኑን እንዳስታወቁት የምርጫው ጊዜ ተቆርጦ ባይወሰንም የመራጮች ምዝገባ ለሚቀጥሉት ሁለት ወራት ድረስ ይካሄዳል፡፡ በውጭ የሚኖሩ ሊቢያዊያንም በኢንተርኔት በቀጥታ ምርጫ ምዝገባው እንደሚካተቱ በተመድ የሊቢያ መልዕክተኛ ገሳን ሰላም ተናግረዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሁለት ተከፍሎ ያለውን የሊቢያ መንግስት እርቅ አውርዶ በአዲስ ምርጫ ፖለቲካዊ ሽግግር እንዲመጣ በመስራት ላይ መሆኑም ይታወቃል፡፡ በሊቢያ እ.ኤ.አ በ2011 በጀመረው ህዝባዊ አመፅ የቀድሞ መሪ ሙዓመር ጋዳፊ ከስልጣን ላይ ተወግደው ከተገደሉ በኋላ፣ እስካአሁን በማያባራ ግጭት ውስጥ ትገኛለች፡፡ ሊቢያም እስካአሁን ወጥ በሆነ መልኩ የሚመራት መንግስት የሌላት አገር ሆና በሽፍቶች መፈንጫነቷ ትታወቃች ፡፡ በቅርቡም መንግስት አልባ በሆነችው በዚህችው ሊቢያ አፍሪካዊያን ስደተኞች በባርነት ሲሸጡ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል መውጣቱ ብዙዎችን ማስቆጣቱም የሚታወስ ነው፡፡

ሽብርተኝነት

አይ.ኤስ በአለም አቀፍ ደረጃ በሽብርተኝነት የተፈረጀ ቡድን ሲሆን መሰረቱን በተለያዩ አገራት አድርጎ የተለያዩ ጥቃቶችን ይፈፅማል፡፡ ቡድኑ ከነበረበት ቦታ እንዲለቅ ቢደረግም በመጪው አዲስ አመት ዳግም እንዳይከሰት ፍራቻ እንዳለ ዘገባው በድረገፁ ገልጿል፡፡ የሽብር ቡድኑ በሶርያና በኢራቅ እንዲሁም በሌሎች ቦታዎች ላይ ጥቃት በማድረስ እንቅስቃሴ መጀመሩን ዘገባው አስታውሷል፡፡ ቡድኑን ለማጥፋት በተደረገው ጥቃት የተረፉ የቡድኑ አባላት ከአልቃይዳ ጋር በመተባበር ወይም እራሳቸውን ችለው ሊመጡ ይችላሉ የሚል ስጋቶች አይለዋል፡፡ በመካከለኛው ምስራቅ በተለይ በሊቢያ፣በሶርያና በኢራቅ አካባቢ በድጋሚ አለመረጋጋቶች ከተፈጠሩ አይ.ኤስ ይሁን ሌላ የሽብር ቡድን የፖለቲካ ሁኔታውን ሊቆጣጠር እንደሚችል ዘገባው ግምቱን አስቀምጧል፡፡ ከላይ የተቀመጡት አምስት ጉዳዮች በአዲሱ የፈረንጆች አመት የሚጠበቁ ጉዳዮች ሲሆኑ በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ በፖለቲካው  ያልተጠበቀ እንቅስቃሴ ሊኖር እንደሚችል ዘገባው ጠቅሷል፡፡

መርድ ክፍሉ

 

Published in ዓለም አቀፍ

ወዛጋቢው ፕሬዚዳንት እያንዳንዱን አረገዋለሁ ያሉትን መተግበራቸውን ቀጥለዋል፡፡ የተለያዩ ወገኖችም ፕሬዚዳንቱ በምርጫ ዘመቻቸው አረጋቸዋለሁ ያሏቸውን እየፈጸሙ መሆናቸውን እየመሰከሩ ናቸው፡፡

ከመጀመሪያው ጥቁር የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ  በትረ ስልጣኑን ልክ የዛሬ ዓመት የተረከቡት 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በየጊዜው በሚያስተላልፏቸው አወዛጋቢ ውሳኔያቸውና በሚፈፅሟቸው የተለየ ድርጊቶች ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ግራ እያጋቡ ይገኛሉ፡፡

   ሃገራቸው ከሜክሲኮ ጋር የምትዋሰንበትን ረጀም ድንበር ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መተላለፊያ ሆኗል በሚል በግምብ አጥረዋለሁ በሚለው አዋዛጋቢ ውሳኔያቸው ጀምረው በስደተኞች ላይም ይህንኑ መቀጠላቸው ይታወቃል፤ ወዲያው ደግሞ በሰሜን ኮርያ ጉዳይ ተጠምደዋል፡፡ ሰሜን ኮርያ በላይ በላይ እንደ ርችት የምታስወነጭፈውን የረጅም ርቅት ሚሳኤል ከምንም ሳይቆጥሩት ቢቆዩም ጉዳዩ እየቆየ እንቅልፍ ነስቷቸዋል፡፡ ለልዕለ ሃያሏ ሀገራቸው ይህን ከባድ ስጋት ለማስወገድ ሰሜን ኮሪያን እንደምታ ጠፋት በተባበሩት መንግሥታት ዓመታዊ ጉባኤ ላይ እስከ መዛትም ደርሰዋል፡፡

    የፕሬዚዳንቱን የተለያዩ ጊዜያት ዛቻ ከመጤፍ ያልቆጠረችው ሰሜን ኮሪያም ሚሳኤል ማስወንጨፏን ቀጥላበታለች፡፡ እጀ ረጅሟ አሜሪካም በቅርቡም ሰሜን ኮሪያን አደብ ያስገዛል ያለችውን የነዳጅ ማእቀብ ጨምሮ በተለያዩ ሀገሮች የሚገኙ ዜጎቿ ወደ ሀገራቸው እንደሚመለሱ የሚያደርግ ውሳኔ በተባባሩት መንግሥታት በኩል አሳልፋለች፡፡

 በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ጠንካራ ድጋፍ አርጋላቸዋለች ለተባለችው  እስራኤል ምስጋና ለመቸር ፕሬዚዳንቱ ሀገሪቱን መጎብኘታቸው ይታወቃል፡፡ በወቅቱም አንድ አወዛጋቢ ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ ሀገራቸው ቴላቪቭ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ወደ እየሩሳሌም እንደምታዘዋውር ቃል በመግባት የእስራኤል ዋና ከተማ እየሩሳሌም መሆኗን የሚያረጋግጥ ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ ይህን ተከትሎም በመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ብቻም ሳይሆን በመላ ዓለም ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።

    እኚሁ አወዛጋቢ ሰው ዛፍ መቁረጥ የሚያደርስ ውሳኔም ሰሞኑን አሳልፈዋል፡፡ ይህ በነጩ ቤተመንግሥት በር ላይ  የሚገኘውን እድሜ ጠገቡን ማኞሊያ ተብሎ የሚጠራውን ዝነኛ ዛፍ ካልተቆረጠ ሞቼ እገኛለሁ እያሉ መሆናቸውን ሰሞኑን ቢቢሲ በድረገፁ ያወጣው ዘገባ አመልክቷል፡፡

     ዘገባው እንዳመለከተው፤ ይህ የሞኞሊያ ዛፍ የ200 ዓመት እድሜ ባለፀጋና ታሪካዊ የነጩ ቤተመንግሥት ዛፍ ሲሆን፣ በዶናልድ ትራምፕ የይቆረጥ ውሳኔ ተላልፎበት ቀን ተቆርጦለት ሞቱን እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡

     «ጃክሰን» ማኞሊያ የተሰኘው ይህ ዛፍ በያኔው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በአንድሪው ጃክሰን አማካኝነት ለቆንጆዋ ባለቤታቸው ችሮታ ይሆን ዘንደ የተተከለ መሆኑን ዘገባው አያይዞ ጠቁሟል፡፡ ከ1928 እስከ 1988 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በአሜሪካ የ20 ዶላር የገንዝብ ኖት ላይ ምስሉ ታትሞ እንደነበርም አመልክቷል፡፡ 

ዛፉ በእርጅና ምክንያት እንዳይወድቅ በሚል የሲሞኒንቶ ምሰሶ ድጋፍ ተደርጎለት እስካሁን የቆየ ቢሆንም፣ ሙሉ በሙሉ ራሱን ችሎ ሊቆም የማይችልና ድንገት ተገንድሶ ሊወድቅ ይችላል የሚል ስጋትም በፕሬዚዳንቱ ላይ አሳድሯል፡፡ ዛፉ ቢወድቅ በእንግዶች ላይ አደጋ ሊያስከትል ይችላል በማለት  ትራምፕ ከእጽዋት ባለሞያዎች ጋር ተማክረው እንዲቆረጥ ውሳኔ ላይ ደርሰዋል።

ዘገባው እንዳብራራው፤ በዚህ ዛፍ የ200 ዓመት እድሜ በነጩ ቤተመንግሥት 39 ፕሬዚዳንቶች ተፈራርቀዋል፡፡ የአሜሪካን ሲቪል ጦርነትን ጨምሮ ሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ተካሂደዋል፡፡  የትራምፕን  የስልጣን ቆይታ ሳያይ መሰናበት የግድ ሆኖበታል፡፡

   የዶናልድ ትራምፕ የዛፉ ይቆረጥ ውሳኔ በነጩ ቤተመንግሥት ይኖሩ የነበሩ ፕሬዚዳንቶችንና ቤተሰቦቻቸውን ግራ አጋብቷል፤ ሰውዬው ግን በእድሜ ጠገቡ ዛፍ ምትክ ሌላ ተመሳሳይ ዛፍ በአቸስኳይ ይተከል በሚል ያሳለፉት ቀጭን ትዛዝ፣ ይሁንታንም አስገኝቶላቸዋል፡፡ ከቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን ልጅ  ቼልሲ ክሊንተን ምስጋና ተችሯቸዋል፡፡

    የነጩ ቤተመንግሥት ቃል አቀባይ ስቴፋኒ ግሪሻን በበኩላቸው ትራምፕ ዛፉ በአስቸኳይ እንዲቆረጥ ትዛዝ እንዳስተላለፉ ገልፀው፣ በምትኩ የዚሁ አይነት የዛፍ ችግኝ እንዲተከል ማዘዛቸውንም አመልክተዋል፡፡

     እንደ ቃል አቀባይዋ ገለፃ፤ ትራምፕ ይህ ታሪካዊ ዛፍ እንዲቆረጥ ውሳኔ ላይ የደረሱት ዛፉ ከማርጀቱ ጋር በተያያዘ ድንገት ቢወድቅ ነጩን ቤተመንግሥት በሚጎበኙ ሰዎችና የጋዜጠኞች አባላት ላይ አደጋ ያደርሳል ከሚል ስጋት ነው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም የእሳቸው ሄሊኮፐተር በሚነሳበት ጊዜ በዛፉ አካባቢ ጎብኚዎችና ጋዜጠኞች ስለማይጠፉ፣ ጉዳት ሊያደርስባቸው   ይችላል የሚል ስጋት አድሮባቸዋል፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

Published in መዝናኛ

በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና፤ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ  የሰላም ማስከበር ሲነሳ የኢትዮጵያም ስም አብሮ ይነሳል፡፡ ስሟ የሚነሳውም ለሰላም ማስከበር ካላት ቁርጠኝነት እንዲሁም በሰላም ማስከበሩ በተጨባጭ ባበረከተቻቸው ተግባሮች የተነሳ ነው፡፡

በአህጉሪቱም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላም አስከባሪዎችን በማሳተፍ ግንባር ቀደም ናት፡፡ ኢትዮጵያዊያን ለአፍሪካዊያን ወንድሞቹ እና ለመላው ዓለም ህዝብ ሰላም ዋጋ ከፍለዋል፡፡  ይህም ሥራው የአንድ ሥርዓት ወይም መንግሥት አቋም ሳይሆን ዘመን የማይሽረው የሀገሪቱ መለያ እስከ መሆን ደርሷል፡፡ ይህ አኩሪ ተግባር በሰላም እጦት የሚታመሱ ሀገሮች ሰላም አስከባሪ እንዲመደብላቸው ሲታሰብ ምርጫቸው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ እንዲሆን እስከ ማድረግም ደርሷል፡፡

የሀገሪቱ የሰላም ማስከበር ታሪክ በ1940ዎቹ ይጀምራል፡፡ ከዚህ ወቅት ጀምሮ በኮሪያ፣ ኮንጎ፣ በኮቲዲቧር፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ላይቤሪያ፣ በሱዳን ዳርፉር፣ በደቡብ ሱዳን እንዲሁም በሶማሊያ ኢትዮጵያዊያን በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ተሳትፈው አኩሪ ተግባር ፈጽመዋል፡፡ ሀገሪቱ ይህን ተግባሯን አሁንም አጠናክራ ቀጥላለች፡፡ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላም አስከባሪዎች በአፍሪካ ህብረት እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ሥር በመሆን በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ሰላም በማስከበር ላይ ይገኛሉ፡፡

የሰላም ማስከበር ተልዕኮዋን የበለጠ ለማጠናከርና ተልዕኮዎቿን በብቃት ሊወጣ የሚችል ባለሙያ ለማፍራት እንዲያስችላትም የሀገሪቱ የሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ማዕከል ከስድስት ዓመታት በፊት አቋቁማለች፡፡ ይህ ማዕከል በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ የሚሰማሩ ኢትዮጵያዊያንን ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ ሰላም አስከባሪዎችን በማሰልጠን በአቅም ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል፡፡ ማዕከሉ ከተለያዩ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በሚገኝ ድጋፍ በግጭት መከላከል እና በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ለሚሳተፉት ተከታታይ ስልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

በቅርቡ በጃፓን መንግሥት የፋይናንስ ድጋፍ እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ቴክኒካዊ ድጋፍ ማዕከሉ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከዘጠኝ የአፍሪካ ሀገራት ለተውጣጡ የመከላከያና የፖሊስ አባላት እንዲሁም ሲቪሎች የተሰጠው ስልጠና ተጠቃሽ ነው፡፡ ለአስር ቀናት በቆየው ስልጠና 23 ከመከላከያ፣ 3 ከፖሊስ እንዲሁም ሶስት ከሲቪል የተውጣጡ በአጠቃላይ 29 ሰልጣኞች የተሳተፉ ሲሆን ከሰልጣኞቹ መካከል ሶስቱ ሴቶች ናቸው፡፡

ስልጠናውም ስለ ግጭት ጽንሰ ሀሳቦች፣ ስለ ግጭት ባህሪያት፣ የግጭት ትንተና መሳሪያዎች፣ ስለ ግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያ፣ ስለማሸማገል እና ማስታረቅ፣ በማሸማገል እና ማስታረቅ ውስጥ በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ሚና፣ የተወሳሰቡ ግጭቶችን መከላከል በሚቻልባቸው መንገዶች፣ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ህጎች እንዲሁም በስርዓተ ጾታ ዙሪያ ያጠነጠነ ነበር፡፡ ሰልጣኞቹ ከኢትዮጵያ፣ ቡሩንዲ፣ ካሜሮን፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ላይቤሪያ፣ ማሊ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን እና ዩጋንዳ የተውጣጡ ናቸው፡፡

ስልጠናው በአህጉሪቱ በተደጋጋሚ የሚከሰቱትን ግጭቶች ለመከላከል፤ መከላከል ካልተቻለም የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር ለማዋል ለሚያደርጉት ጥረት እገዛው ላቅ ያለ መሆኑን ሰልጣኞቹ ተናግረዋል፡፡

ሰልጣኞችን ወክለው ስለ ስልጠናው አስተያየት የሰጡት ብርጌደር ጄኔራል ታደሰ አመሉ እንዳሉት፤ ስልጠናው ስለ ግጭት አፈታት ዘዴዎች ሰልጣኞቹ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡ ከአቅም በላይ በሆኑ ምክንያቶች ግጭቶች ሲከሰቱ ወደ አስከፊ ደረጃ እንዳይደርሱ ምን መደረግ እንዳለበት ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ኮርሶች ተሰጥተዋል ፡፡

 የግጭቶች ትንተና መሳሪያዎች፣ ባላንጣ ወገኖችን የማደራደር እና የማሸማገል ሥልጠናዎችንም እንዳገኙ የሚናገሩት ብርጌደር ጄኔራል ታደሰ፣ በቀጣይ ችግሮች በሚከሰቱበት ወቅት ሁሉም ሰልጣኝ ያገኘውን እውቀት እየመነዘረ ለአህጉሪቱ ሰላም የበኩሉን እንዲወጣ የሚያስችል መሆኑን ይናገራሉ። «ሰልጣኞቹ ከተለያዩ ሀገራት እና ዘርፎች የተውጣጡ እንደመሆናቸው እርስ በእርስ ለማማር እድል ፈጥሮላቸዋል።»

ከሩዋንዳ በስልጠናው ላይ የተሳተፉት ሜጀር ጀኔራል ዊልሰን ሯንጓ በተለይ ለአዲስ ዘመን  በሰጡት አስተያየት ግጭት በመላው ዓለምም ሆነ በአፍሪካ መከሰቱን ሙሉ በሙሉ ማስቆም የማይቻል ክስተት መሆኑን ጠቅሰው፣ ስልጠናው በጣም አስተማሪ፣ ሰልጣኞችም ለሰላም ማስከበር አስፈላጊ የሆነውን ሁሉ እውቀት እና ክህሎት ማግኘት የቻሉበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

 እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ሀገራት ሰላም አስከባሪዎችን እንደሚልኩ ሁሉ ሩዋንዳ ለተባበሩት መንግሥታት ሰላም ማስከበር ተልእኮ ሰላምን ለማስፈን ወታደር እንደምታዋጣ ሜጀር ጀነራሉ ይገልጻሉ፡፡ እሳቸውም ወታደር እንደመሆናቸው በአፍሪካ ህብረትም ሆነ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥላ ሥር ሰላም ለማስከበር በሚሰማሩበት ወቅት ስልጠናው እገዛ እንደሚያደርግላቸው አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ ሰላም አስከባሪዎችን በማሳተፍ ለአፍሪካ ሰላም የምታበረክተው ሚና ከፍተኛ ነው ያሉት ሜጀር ጄኔራል ዊልሰን፣ አሁን ደግሞ ከተለያዩ ሀገራት እና ድርጅቶች ጋር በመሆን ለሰላም አስከባሪዎች አቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎችን መስጠት መጀመሯ ለአህጉሪቱ ሰላም እና መረጋጋት ያላትን ጽኑ አቋሟን አመላካች ነው ብለዋል፡፡

በጃፓን መከላከያ የምድር ጦር መኮንን ሌተናል ኮሎኔል ኖሪሂሳ ዩራካሚ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲሁም በአፍሪካ ህብረት ሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በርካታ ሰላም አስከባሪዎች በማበርከት ቀዳሚ  ሀገር ናት፡፡ በምስራቅ አፍሪካና በመላው አህጉሪቱም ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የምታበረክተው ጥረት የሚያስመሰግናት ነው፡፡ በተለይም የሰላም ማስበር ሥልጠና ማዕከል ማቋቋሟ ለሰላም ማስከበር የምታደርገውን ጥረት እንድታጠናክር እገዛ አድርጓል፡፡

ከማዕከሉ ጋር በመተባበር የጃፓን መንግሥት ከአምስት ዓመታት ወዲህ ለአህጉሪቱ ሰላም አስከባሪዎች ሥልጠናዎችን እየሰጠ ነው፡፡ በቅርቡ የተሰጠውን ጨምሮ ሰባት ዙር ሥልጠናዎችን ሰጥቷል፡፡ ሥልጠናዎቹም ስኬታማ እንደነበሩ ያወሱት ኮሎኔል ራካሚ በሰባተኛ ዙር የተሰጠው ሥልጠናም ሥልጠና ስለ ግጭቶች መሰረታዊ ፅንሰ ሀሳቦች፣ ስለ ባህሪያቱ፣ ስለ ሚያሳድረው ተጽዕኖ፣ የግጭት መገለጫዎች ላይ ያጠነጠነ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ሌተናል ኮሎኔል ዩራካሚ እንደሚሉት፤ በሥልጠናው በተለይም ስለዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ፣ ስለ ህግ የበላይነት፣ ስለህጻናት እና ሴቶች መብት አጠባበቅ እና በዚህ ወቅት ስለሚያጋጥሙት ተግዳሮቶች እንዲሁም ስለቅድመ ግጭት መከላከል እውቀት አግኝተዋል፡፡

እሳቸውም የሰላም አስከባሪዎቹ ግጭቶችን ቀድሞ የመከላከል፣ የማሸማገል እንዲሁም የማደራደር አቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥልጠናዎችን መውሰዳቸውን ይናገራሉ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በቀጣናዊ የሰላም ማስከበር ተቋማት ውስጥ ስላላቸው ሚና ግንዛቤ የሚስያጨብጡ ኮርሶች የሥልጠናው አካል እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡

ማዕከሉ የሚሰጣቸው ሥልጠናዎች ሰላም አስከባሪዎች ከኢትዮጵያ አልፎ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ማለትም በቀጣናዊ እና በአህጉራዊ ተልዕኮዎች ላይ በብቃት እንዲሳተፉ የሚያደርግ ነው፡፡

ማዕከሉ የአፍሪካን ተጠንቀቅ ኃይል አቅም ለማጠናከር ጭምር እገዛው እንደሚያደርግ አመልክተው፣ ሥልጠናዎቹ በሌክቸር፣ በልምምድ እንዲሁም በካርታ አጠቃቀም ዙሪያም የሚያተኩሩ በመሆናቸው ሰልጣኞቹ የቀሰሙትን እውቀት በተግባር ለመለወጥ አይቸገሩም ብለዋል፡፡

የሰላም ማስከበር የሥልጠና ማዕከል ኃላፊ ብርጌደር ጄኔራል ሀብታሙ ጥላሁን እንደተናገሩት፤ ሰልጣኞቹ ያገኙት ሥልጠና በአፍሪካ ችግሮች በሚከሰቱበት ጊዜ በአግባቡ ለመቆጣጠር  የሚያስችል አቅም ይፈጥርላቸዋል፡፡ በአፍሪካ የሚከሰቱ ግጭቶችን በአግባቡ መስመር የሚያሲይዝ አካል ካልተገኘ ግጭቶቹ ቀጣይነት ሊኖራቸው  ይችላል፡፡ እስካሁን እንደታየውም በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ማብቂያ አይኖረውም፡፡

በመሆኑም በአህጉሪቱ ወደ ፊት ሊከሰቱ የሚችሉ የሰላም እና ደህንነት ችግሮችን ለመፍታት የሚችሉ እጩ ሰላም አስከባሪዎች እና ግጭቶችን በመፍታት ላይ ለሚሰሩ ለሌሎች አካላት የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንዲያገኙ ማድረግ ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳይ ነው ያሉት ኃላፊው፣ ሰልጣኞቹ ውስብስብ በሆኑ የግጭት መከላከል እና ስለግጭት ትንታኔ መሳሪዎች በቂ ሥልጣና አግኝተዋል ይላሉ፡፡ ይህም ግጭቶችን ለመፍታት የሚያስችል እውቀት እና ክህሎት በማሳደግ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአፍሪካ ህብረት የሰላም ማስበር ተልዕኮዎችን ለማሳካት እገዛ እንደሚኖረው አስታውቀዋል፡፡

ሰልጣኞቹ በሥልጠናው የቀሰሙትን ዕውቀት እና ክህሎት በተግባር በማዋል ለአህጉሪቱ ሰላም የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክሩ ጥሪ ያቀረቡት ብርጌደር ጄኔራል ሀብታሙ፤ ሰልጣኞቹ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ እንደመሆናቸው እውቀት እና ክህሎታቸውን እንዲሁም ወንድማዊ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበት እድል የፈጠረ ሥልጠና እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ከሰልጣኞቹ የሚቀርብ ግብረ መልስ እንደ ግብዓት በመጠቀም ማዕከሉ የሥልጠናውን ጥራት የማሳደግ እቅድ እንዳለው የጠቀሱት ብርጌደር ጄኔራል ሀብታሙ፣ በቀጣይም መሰል ሥልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡

  መላኩ ኤሮሴ

Published in ፖለቲካ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቁጥጥር እና ክትትል ሥራውን የሚቀርብለትን ሪፖርት በማዳመጥ እንዲሁም የመስክ ጉብኝት በማድረግ  ያካሂዳል፡፡ በሪፖርቱ የቀረበለትን አፈጻጸም በቦታው ላይ በመገኘት እያረጋገጠ አፈጻጸሙ ዝቀተኛ ከሆነም ለምን ዝቅተኛ እንደሆነ ይጠይቃል፡፡ አፈጻጸሙ ጠንካራ ከሆነ ደግሞ ያበረታታል፡፡

ከምክር ቤቱ የኢንደስትሪ ጉዳዮች ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ መኩዬ ጋር ቃለ ምልልስ ባደረግንበት ወቅት እንዳሉትም፤ ቋሚ ኮሚቴው የኢንደስትሪ ፓርኮች የግንባታ ሂደትን የመቆጣጠርና የመከታተል ኃላፊነቱን ሲወጣ ቆይቷል፡፡

 ወደ ኢንደስትሪ መር ለሚደረገው የኢኮኖሚ ሽግግር የኢንደስትሪ ፓርኮች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፣ ፓርኮቹም እየተገነቡ የሚገኙት የባለሀብቶች ጥያቄ ለነበረው የመሰረተ ልማት ጥያቄ ምላሽ በሚሸጥ መልኩ ነው፡፡ ይህ ሥራ እንደ ጅምሩ ተጠናክሮ ሊቀጥል  ይገባል፡፡

አቶ ብርሃኑ ለኢንደስትሪው የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል የማዘጋጀት፣ በአመለካከት የመቅረጽ  ሥራም እንደሚያስፈልግ እንዲሁም በዘርፉ የቅንጅት አለመፈጠር፣ የእቅድና አፈጻጸም መራራቅ መስተዋሉን፣  የጋራ ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ አሰራር በመዘርጋት በኩል ክፍተቶች እንዳሉም ይናገራሉ፡፡ ቋሚ ኮሚቴው በኢንዱስትሪ ዘርፍ ያደረገው የክትትል እና የቁጥጥር ሥራ  እንደሚ መስል ያነሳንላቸውን ጥያቄዎች እና የሰጡንን ምላሽ ይዘን ቀርበናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የመስክ ምልከታ፣ ጉብኝት እንዲሁም ክትትልና ድጋፍ ምን ፋይዳ አለው? እስካሁንስ ምን ውጤት አስገኝቷል?

አቶ ብርሃኑ፡- የመስክ ምልከታና ጉብኝት ዋናው ፋይዳ የምንከታተላቸው መስሪያ ቤቶች በተለያዩ ሩብ ዓመታት የሚያቀርቧቸው እና የሚልኳቸው የቃልና የጽሁፍ ሪፖርቶች በትክክል እየተፈጸሙ ስለመሆናቸው ማረጋገጥ ነው፡፡ በዚህ ረገድም ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ከዚህ በመነሳት በሚቀጥሉት የሪፖርትና የግምገማ ጊዜያት ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት አድርጎ ሪፖርቱን ለመረዳትና በዚያ ልክ ተግባሩን ለመከታተል ፋይዳው የጎላ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በመስክ ጉብኝታችሁ በምትከታ ተሏቸው ተቋማት የተመለከታ ችኋቸው ዋና ዋና ክፍተቶች እንዲሁም አጠቃላይ ሁኔታዎች ምን ይመስላሉ?

አቶ ብርሃኑ፡-  የመስክ ጉብኝት የሚካሄደው ክፍተቶችን ለመለየት ብቻ አይደለም፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት የሚቀርቡ የቃልና የጽሁፍ ሪፖርቶች በተግባር ምን እንደሚመስሉ የማረጋገጥ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ባለፈው ዓመት ያካሄድናቸው የመስክ ጉብኝቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል በዋናነት እና ሰፋ ባለ መልኩ የመስክ ምልከታ ያካሄድነው በሀዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክ ነው፡፡

የፖርኩ የግንባታና ባለሀብቶች ወደ ፓርኩ የመግባታቸው ሂደት ምን እንደሚመስል ለማየት ተሞክሯል፡፡ በወቅቱም ፓርኩ ከተገነባ በኋላ የተወሰኑ ወራት ባለሀብቶች ወደ ፓርኩ ሳይገቡ መቆየታቸውን አስተውለናል፡፡ አስፈጻሚው አካል በእዚህ ረገድ መስራት ያለበት መሆኑንም ከምልከታችን በመነሳት አመላክተናል፡፡ በዚህ ላይ በመመስረት በተደረገው ትግበራ ባለሃብቶች ወደ ፓርኩ የመግባት እንቅስቃሴያቸው የተሻለ ለውጥ ታይቶበታል፡፡

በሌላ በኩል የሀዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክ ግንባታ አፈጻጸሙ በጣም ፈጣን ነበረ፡፡ ለሌሎቹ የኢንደስትሪ ፓርኮች ግንባታም ልምድ ሊወሰድበት የሚገባ ነው፡፡ ግንባታው በተለይም ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ተያይዞ የነበረው አፈጻጸም ለየት ያለ እና ለሌሎቹ አካባቢዎችም ምሳሌ መሆን የሚችል እንደመሆኑ ቋሚ ኮሚቴውም ፈጣን የፓርክ ግንባታ ሁኔታውንና ጥሩ የኢንደስትሪ ፓርክ ምን ይዘቶች እንደሚኖሩት ለመረዳት ችሏል፡፡ ሌሎቹም በእዚህ መንገድ እየሄዱ ስለመሆናቸው ለማረጋገጥ ጥሩ ትምህርት ወስደንበታል፡፡

የመስክ ምልከታው በተለይም ሪፖርታቸው በሚቀርብበት ጊዜ ሂደታቸውን መገምገም እና መረዳት አስችሎናል፡፡ በመሆኑም ይሄ በመስክ ምልከታው በተጨባጭ ቦታው ላይ ሄደን ካገኘናቸው እውቀቶችና ልምዶች በመነሳት በቀጣይ የሚሰሩ ሥራዎችን እንድንመለከት እድል የሰጠ ነበር ለማለት ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በተመሳሳይ መልኩ ሌላ ምልከታ ያደረጋችሁበት ዘርፍ ካለ ቢነግሩኝ?

 በስጋ ዘርፍ የስጋና ወተት ኢንደስትሪ ልማት የሚሰራቸውንና የሚሰጣቸውን ድጋፎች በሚመለከት ምልከታ አድርገናል፡፡ አገሪቱ ስጋ ወደ ውጭ በመላክ ልታገኝ የሚገባትን የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት እንድትችል እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች ምን እንደሚመስሉ ተመልክተናል፡፡ በተለይ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ግንባታቸውን ጨርሰው አፈጻጸም ላይ ለመግባት የሚያጋጥማቸው የኃይል አቅርቦትና የመሳሰሉ ችግሮችን ለመለየት ችለናል፡፡

ከወተት ሃብት ልማት ጋር ተያይዞም በተለይ በአርብቶ አደር አካባቢ ያለውን የእንስሳት ሃብት የወተት ምርት ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልበትን ሁኔታ አርብቶ አደሮቹ በተለያዩ ማህበራት ተቀባይነት አማካኝነት ከእንሰሳቶቻቸው የሚገኘውን የወተት ሃብት ወደ ፋብሪካ ሊያቀርቡ የሚችሉበት ትስስር መፈጠሩን ተመልክተናል፡፡ ይህ አይነት ሥራ በቀጣይም መጠናከር የሚገባው ተግባር መሆኑን  በአካል ተገኝተን ለማረጋገጥ ችለናል፡፡

በሌላ በኩል እንስሳት ሃብት ላይ ሊሰራ የሚገባውን በተለይ ባለፈው ዓመት ቀድሞ በነበረው የድርቅ ሁኔታ አርብቶ አደሮች አካባቢ ያለው የስጋ ፋብሪካ የአቅርቦት ተጽእኖ አሳድሮ እንደነበር ተረድተናል፡፡ ስለሆነም ዘላቂ የእንስሳት ሃብት ልማት የመገንባት ጉዳይ የስጋ ኢንደስትሪውን በማስቀጠል በኩል ትልቅ ፋይዳ እንዳለው በተግባር ማየት የተቻለበት ሁኔታም አለ፡፡ በመሆኑም በእዚህ አካባቢ በቀጣይ አተኩሮ እንዲሰራ ግንዛቤም የተያዘበት ነው፡፡ 

አዲስ ዘመን፡- በምልከታችሁ በአፈጻጸም ሂደት የምትመለከቷቸውን የመሰረተ ልማት አቅርቦት ችግሮች ለመፍታት የምታደርጉት ድጋፍ ምን ይመስላል?   

አቶ ብርሃኑ፡- በኃይል አቅርቦት ችግር ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት ለማመልከት ሞክረናል፡፡ በእዚህ ዓመት መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት የሰጠው በኢንደስትሪ አካባቢ የኃይል አቅርቦት ቅድሚያ የሚዳረስበትን መንገድ ነው፡፡

በእንስሳት ሃብት ላይም አቅርቦቱ አሁን ካለበት ደረጃ መሻሻል እንዲያሳይ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ለማየት ችለናል፡፡

አገሪቱ ውስጥ ያለውን የእንስሳት ሃብት አሟጦ መጠቀም የሚቻልበት ሁኔታ እንዲኖር የእንስሳት ሃብት ባለበት አካባቢ የተጠናከሩ ማህበራት እንዲደራጁ ማድረግና እንስሳት ወደ ፋብሪካዎች እንዲቀርቡ የሚደረግበትን ስርዓት ማጠናከር እንደሚገባ ታምኖበታል፡፡  እነዚህን ሥራዎች ለመስራት መንግሥት አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡ በእዚህ መሰረትም ሥራዎች እየተሰሩ ሲሆን፣ አንጻራዊ መሻሻሎችም እየታዩ ናቸው፡፡

በእርግጥ በስጋ ዘርፉ ላይ አሁንም የፋብሪካዎች መጠንና የአቅርቦት ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ ልዮነት አለው፡፡ በቀጣይም መሰራት የሚገባው ሥራም አለ፡፡ ግን አንድ አካበቢን ብቻ መሰረት አድርጎ ሳይሆን በትስስር አቅርቦቱ የሚጠናከርበት ሁኔታ መፍጠር ይገባል፡፡ በተለይም ከአባቢያዊ ማህበራት በዚህ ተግባር ላይ ተሰማርተው እንስሶቹን ወደ ትክክለኛው የገበያ አቅጣጫ ሊያመጡ የሚችሉበት መንገድ መፈጠር እንዳለበት አስተያየት አቅርበናል፡፡ በዚህ አግባብም የተጀመሩ ሥራዎች አሉ፡፡ 

አዲስ ዘመን፡- በሪፖርት ደረጃ ተሰርቷል ተብሎ ቀርቦላችሁ በአካል ተገኝታችሁ ስትገመግሙ ግን ያልተፈጸመ ብላችሁ የገመገማችሁት ወይም መሰል ገጠመኝ አልያም መሻሻሎች ካሉ ቢነገግሩኝ? 

አቶ ብርሃኑ፡- እኛ በምንከታተላቸው ተቋማት በሪፖርት ደረጃ ቀርቦ ግን በተግባር ያልተፈጸመ ብለን  የገመገምነው የለም፡፡ በኢንደስትሪ ዘርፉ ላይ ያጋጥም የነበረው ችግር በተለይ የአፈጻጸም መውረድ ነው፡፡ በከፍተኛ ደረጃ እቅድና አፈጻጸም መራራቅ ተስተውሏል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የኢንደስትሪ ዘርፉ የተለያዩ አካላት ቅንጅትን  ስለሚፈልግ ነው፡፡ ዘርፉ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ግብአት፣ የሰው ኃይል፣ መሬት፣ ውሃ፣ የተሟላ  መሰረተ ልማት በከፍተኛ ደረጃ ይፈልጋል፡፡ እነዚህ ነገሮች ሁሉ መቀናጀት አለባቸው፡፡ ስለዚህ በዘርፉ ትልቅ ችግር የነበረው ቅንጅት መፍጠር ነው፡፡ መሻሻልና ለውጥ ማሳየት ላይ ችግር ነበር፡፡

ይህ ሥራ በኢንደስትሪ ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን በሌሎች ተቋማትም መሰራት ያለበት የጋራ ሥራ  ነው፡፡ ችግሩን ተቀናጅቶ መፍታት እንዲቻል የሚመለከታቸውን ሁሉ ጎትጉቷል፡፡ የጋራ ተጠያቂነት የሚያረጋግጥ አሰራር በመዘርጋት በኩል የሚቀር ነገር መኖሩን ማየት ችለናል፡፡

ችግርን የሚፈታ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ በኩል የሚቀር ነገር አለ፡፡ አሁን ይህ ሁኔታ መቀየር አለበት፡፡ የሚመለከተው አካል ለዘርፉ መስጠት የሚገባውን ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ካልሆነ ደግሞ ተጠያቂነት መኖር አለበት፡፡ ይህንንም ቋሚ ቆሚቴው በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ የሚከታ ተለውና ተፈጻሚ መሆንም ያለበት ጉዳይ ነው፡፡  

አዲስ ዘመን፡- ቋሚ ኮሚቴው እስካሁን ባደረጋቸው ክትትልና ድጋፎች በመነሳት የተሻሻሉ፣  የተለወጡ እና ውጤታማ የሆኑ ወይንም በጉድለት የምታነሷቸው አሰራሮች ካሉ ቢነግሩኝ?

አቶ ብርሃኑ፡- በዘርፉ ትልቁና በዋናነት ይነሳ የነበረው የመሰረተ ልማት አቅርቦት ችግር ነው፡፡ ከኢንደስትሪ ፓርክ ጋር ተያይዞ ችግሩ እየተፈታ ይገኛል፡፡ ባለሃብቱ ወደ ፓርኩ ከመግባቱ በፊት ወይንም ጎን ለጎን መሰረተ ልማት የሚሟላበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በመሆኑም በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ባለሃብቱ ያነሳቸው የነበሩ የውሃ፣ የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ አቅርቦቶች አስቀድሞ ተጠናቅቀዋል፡፡ ዝግጁ በሆነ ስፍራ ላይ ባለሃብቶች እየገቡ ናቸው፡፡ ስለዚህ በዘርፉ ቀድሞ ይነሳ የነበረው ቅሬታ ተወግዷል ማለት ይቻላል፡፡

በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ሁለት የኢንደስትሪ ፓርኮች ለመገንባት

እንኳን በጣም አስቸጋሪ ነበረ፡፡ አሁን በርካታ የኢንደስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ ናቸው፡፡ ይህም የሁሉም አካላት ሃሳብና ውጤታማነት መገለጫ ነው፡፡

ሌላው ጥሩ ሥራ ተብሎ የሚወሰደው ኢንቨስትመንት መስኮች የሚሰማራ ባለሃብት መሳብ ነው፡፡ በተለይ አቅም እና ልምድ ያላቸው እንዲሁም በዓለም ገበያ ገብተው ትልቅ አስተዋጽኦ  እያበረከቱ የሚገኙ ኩባንያዎች አገር ውስጥ ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ እንዲሁም የገበያና የክህሎት ችግሮችን አቃልሎ ማለፍ እንዲቻል እየተሰራ ያለው ሥራ ውጤታማ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አፈጻጸሙም መሻሻል አሳይቷል፡፡

አዲስ ዘመን፡- እንደ አገር ከግብርና ወደ ኢንደስትሪ መር የኢኮኖሚ ሽግግር እየተደረገ ይገኛል፡፡ ወደ ኢንደስትሪ የሚደረገውን ሽግግር የሚያደናቅፍ እና በአሰራርም ወደሚፈለገው ደረጃ ለመሸጋገር እንቅፋት ይሆናሉ ብላችሁ የለያችኋቸው ተግዳሮቶች አሉን?    

አቶ ብርሃኑ፡- ትልቁ ችግር የነበረው እና አሁንም ያልተፈታው የኢንደስትሪ ግብአት ነው፡፡ ይህ በቀጣይም ትልቅ ርብርብ ይፈልጋል፡፡ በአገራችን ሁኔታ ግብርና እና ኢንደስትሪን እናስተሳስራለን ስንል አግሮ ኢንደስትሪ ላይ እናተኩራለን ማለታችን ነው፡፡ ስለዚህ በአግሮ ኢንደስትሪው በግብርናው ዘርፍ ለኢንደስትሪ የሚያስፈልገውን ግብአት በአይነት፣ በጥራት፣ በመጠን ለማቅረቡ ሥራ ትልቅ ትኩረት ይሰጣል፡፡ መንግሥትም ትኩረት ሰጥቶ የጀመራቸው ሥራዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ የአግሮ ኢንደስትሪ ፓርኮች ለዚህ ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ በመሆኑም በአንድ መቶ ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ ከግብርና ጋር ተመጋጋቢ የሚሆኑበት ሁኔታ እንዲፈጠር በማድረግ ላይ ተመስርቶ እየተሰራ ነው፡፡

በጥጥ፣ በቆዳና በሌሎቹም የግብርና ምርቶች ማቀነባበር ለሚሰማሩ ኢንዱስትሪዎች ወሳኝ ተደርጎ የሚወሰደው ግብዓት እንደመሆኑ እዚህ ላይ መረባረብ ያስፈልጋል፡፡ መሰረተ ልማት እያሟላን ባለሃብት እያስገባን እንገኛለን፡፡ ለኢንደስትሪው በጣም አስፈላጊው የሰው ኃይል ክህሎት በጣም ወሳኝ ነው፡፡ በዘርፉ የሚሳተፍ የሰው ኃይል በጣም በርካታ ነው፡፡ በመሆኑም የኢንደስትሪ አስተሳሰብ፣ ዝግጁነት እና ባህል ያዳበረ ብቁ ባለሙያ መታሰብ አለበት፡፡ ስለዚህ የህብረተሰቡ ቁርጠኝነት፣ የሰራተኛው ዝግጁነት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በመሆኑም ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ገበያ የማፈላለግና የማስተሳሰር ሥራ መስራትም በጣም ወሳኝ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ከውጭ ባለሃብት ጋር ተሳስረው የሚሰሩበት በቀጣይ ራሳቸው ገበያ ማግኘት የሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል፡፡

አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለኢንደስትሪው መሰረት ናቸው፡፡ እነዚህ ቁጥራቸው በርካታ ስለሚሆን በመሰረተ ልማት የመደገፍ ሥራ በየአካባቢው መሰራት ይኖርበታል፡፡ የየራሳቸው ክላስተር እንዲኖራቸው በማድረግም መደገፍ ያስፈልጋል፡፡    

አዲስ ዘመን፡- እየተገነቡ የሚገኙት ፓርኮች ሥራቸውን አጠናቅቀው ወደ ምርት ሲሸጋገሩ የኃይል አቅርቦት እንቅፋት እንዳይሆንባቸው ምን የታሰበ ነገር አለ?   

አቶ ብርሃኑ፡- ይህንን በሚመለከት ጎን ለጎን እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች አሉ፡፡ በተለይም ከ2009 ዓ.ም አራተኛ ሩብ ዓመት በኋላ መንግሥት ፓርኮች አካባቢ የኃይል አቅርቦትን በተመለከተ ትኩረት ሰጥቶ እልባት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ አካባቢዎቹ የኢንደስትሪ ማዕከላት እንደመሆናቸው ቅድሚያ ይሰጣቸዋል፡፡ በመሆኑም በልዩ ሁኔታ አቅርቦት እንዲደረግ ተወስኖ እየተሰራ ነው፡፡

በተለይም ግንባታቸው አልቆ ወደ ሥራ የሚገቡት ፓርኮች የኃይል አቅርቦት ለሥራቸው ወይም ለምርት እንቅፋት እንዳይሆንባቸው ቅድሚያ አግኝተው የኃይል አቅርቦት እንዲያገኙ የኃይል አቅርቦትና የመሰረተ ልማት ሥራ የሚሰራበትን ሁኔታ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ግንባታቸው እየተሰራ ሲሆን ከዚህ ጎን ለጎንም አቅርቦቱ የሚቀጥል ይሆናል፡፡  

አዲስ ዘመን፡- የየአካቢዎቹን እምቅ አቅም መሰረት አድርገው እየተቋቋሙ ላሉ ፓርኮች የመሰረተ ልማት በሟሟላት በኩል መንግሥት እየወሰዳቸው የሚገኙ እርምጃዎች ምን ይመስላሉ?

አቶ ብርሃኑ፡- ፓርኮች ስንል ሁለት አይነት ናቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ አንደኛው አግሮ ኢንደስትሪ ፓርከ ነው፡፡ አግሮ ኢንደስትሪ ፓርኮች በአነስተኛ እና መካከለኛ ፋብሪካ ደረጃ ይሰራሉ፡፡ አሁን በግንባታ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ እነዚህ ናቸው ከአካባቢው ግብርና ጋር በፍጥነት የሚያያዙት፡፡ ከግንባታው ጎን ለጎንም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የግብዓት አቅርቦትን ታሳቢ በማድረግ እየተሰራ ሩገኛል፡፡ 

በአገር ደረጃ ያለው የኢንደስትሪ ፓርክ ባለሀብቶቹ ትላልቅ ናቸው፡፡ ግብዓትን በሚመለከት በአገር ውስጥ የሚገኘውን ያህል እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ቀሪው ከውጭ በሚገባው እንደሚሰሩ ይታሰባል፡፡ ፋብሪካዎቹን ሙሉ በሙሉ በግብዓት መሸፈን የሚቻልበት ደረጃ ላይ አይደለንም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከግብርና መር ወደ ኢንደስትሪ የሚደረገው ሽግግር በታቀደው መልኩ ይሳካል ይላሉ? በምልከታችሁስ ያረጋገጣችሁት ነገር ምን ይመስላል?

አቶ ብርሃኑ፡- መዋቅራዊ ለውጥ ሲታሰብ በራሱ ብቻውን ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፡፡ ከሌሎች ዘርፎች እድገት ጋር አብሮ የሚመጣ ነው፡፡ ግብርና ለኢንደስትሪው ግብአት ሲያመርት በመጠን፣ በአይነት፣ በቦታ ማምረት ሥራ ውስጥ ሲገባ ለኢንደስትሪ ግብዓት የመሆን ብቃቱ አብሮ ይመጣል፡፡ ስለዚህ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሲመዘን በመጠን በማሳደግ ብቻ አይደለም፡፡ ለኢንደስትሪ በሚሆን አይነት ነው የራሱ ውስጣዊ መዋቅራዊ ለውጥ የሚያመጣው፡፡ በመሆኑም ተነጣጥሎ የሚታይ አይደለም ትስስር አለው ማለት ነው፡፡

ግብርናው በትክክለኛ መንገድ እስከሄደ ድረስ ኢንደስትሪውም በትክክለኛ መንገድ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ኢንደስትሪዎች ለሚፈልጉት የሰው ኃይል ቴክኒክና ሙያዎች የሰው ኃይል የማዘጋጀት በአስተሳሰብ የመቅረጽ  ሥራ ውስጥ መግባት ይኖርባቸዋል፡፡ ፓርኮቹ በፍጥነት እተጠናቀቁ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ለባለሀብቶች እንቅፋት ሳይሆኑ ተግባራዊነቱ እንዲጀምሩ መቀጠል ይኖርበታል፡፡

እነዚህን እያደረግን ስንቀጥል ሽግግር ይመጣል፡፡ ትራንስፎርሜሽን ሂደት ነው፡፡ ኢንደስትሪው በኢኮኖሚው ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዝበት ባህሪ ነው፡፡

የማህበረሰቡ አኗኗርም በዘርፉ የጎላ ሚና እንዲኖረው የማድረግ ነገር ይኖራል፡፡ ይህ በአንድ ጀምበር የሚከሰት ሳይሆን በሂደት በሽግግር የሚፈጠር ነው፡፡ በእዚህ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ሙሉ በሙሉ ሰፊውን የኢኮኖሚ ድርሻ ኢንደስትሪ ይይዛል የሚል አላማ የለም፡፡ ግን መሰረት የሚጣልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ በተለይም ወደ ሶስተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ሽግግር ኢንደስትሪው ጋር የሚጠበቁ ታላላቅ ኢንደስትሪዎችም ጭምር ለመገንባት መሰረት የምንጥልበት ሁኔታ እየተፈጠረ ይሄዳል፡፡ በመሆኑም ሽግግሩ ይሳካል የሚል እምነት አለኝ፡፡         

አዲስ ዘመን፡- በዘርፉ በስጋት ደረጃ የሚጠቁሙት ካለ?

አቶ ብርሃኑ፡- በስጋት ሊቀመጡ ከሚችሉት መካከል አንዱ ግብርናችን በተፈጥሮ ጥገኝነት ስር ያለ መሆኑ ነው፡፡ የግብርናው ውጤታማነት የዘርፉ የስኬት መሰረት እንደመሆኑ ከዝናብ ጋር የተያያዙት ሥራዎች ችግር ካጋጠማቸው እንደ ስጋት ይወሰዳል፡፡ በመሆኑም ግብርናችን ወደ መስኖ የሚሸጋገርበት ሥራ በትኩረት መሰራት ይኖርበታል፡፡ ይህ ከተከናወነ በየዓመቱ አስተማማኝ ነገር እየተፈጠረ ይሄዳል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ እያጋጠሙን እንዳሉት አይነት በየአጋጣሚው የሚፈጠሩ ግጭቶች አለመግባባቶችና የመሳሰሉ ጉዳዮች መወገድ አለባቸው፡፡ ይህ አይነት ተግባር የኢኮኖሚ ትስስሩን፣ የግብአት ዝውውሩን አጠቃላይ ገበያውን፣ ባለሃብት ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ከማድረግና ኢንቨስትመንትን ከመሳብ አኳያ ጥላሸት ይቀባል፡፡ በመሆኑም እንደዚህ አይነት ችግሮች መወገድ አለባቸው፡፡

ክህሎት ለኢንደስትሪ የተመቸ እንዲሆን ከማድረግ አኳያም ሌት ከቀን መስራት ያስፈልገናል፡፡ ሽግግሩን እንዲሁ በቀላሉ የምናረጋግጠው ጉዳይ አይደለም፡፡ ውጤቱን ማምጣት የምንችለው በሥራ ወይም በትግል ነው፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ምዕራባውያን አገራት አሮጌውን ዓመት ሸኝተው አዲሱን ዓመት ከተቀበሉ እንሆ ዛሬ ሁለተኛ ቀናቸውን ጀምረዋል። ከቀናት በፊት ዘንድሮ የተባለው 2017ም ቦታውን ለባለ  ተራው 2018 ለቅቋል። ዓለማችንም ባሳለፍነው ዓመት ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስኬቶች አስመዝግባለች፤ ፈተናዎችን ተጋፍጣለች። ዘንድሮስ በተለይ በፖለቲካው ዓለም ምን ታሳየን ይሆን?

እንደ ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘገባ ከሆነ ይህ ዓመት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተጨማሪና አወዛጋቢ ውሳኔዎችን የሚያሳልፉበት በዚህም ከባድ ፈተና የሚገጥማቸው ዓመት ነው። በተለይ የአሜሪካና የሰሜን ኮሪያ ጉዳይ እንደ ዓምና እና ካቻምናው ሆኖ ዘንድሮም ይቀጥላል።

ዘንድሮም ሰሜን ኮሪያ የባልስቲክ ሚሳኤል ሙከራዋን ይበልጥ የምትቀጥልበት፤ ትራምፕ በአንፃሩ የፒዮንግያንግ መንግሥት፤ እልሃችንን እያስጨረሰን ነው» በሚል የአገሪቱን ተግባር በቲውተር ገፃቸው ደጋግመው የሚያወግዙበት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። የሁለቱ አገራት መሪዎች በዚህ መልኩ ማዶ ለማዶ ከመዘላለፍ በዘለለ ልባቸው አብጦ ወደ ጦርነት ይገባሉ ብሎ ማሰብ ግን ሞኝነት ይሆናል።

ከዚህ በተጓዳኝ ቻይና የበረታ ጡንቻዋን በጃፓን ላይ ለማሳየት የምትዳዳውም በሌላ ሳይሆን በዚሁ ዓመት ነው። በተለይ በጃፓን የባህር ቀጣናዎች የተለያዩ የቅኝት በረራዎች የምታደርግ ሲሆን፣ ይህም  ለጃፓናውያን ስሜታዊነት ምክንያት ሲሆን መመልከታችን አይቀሬ ነው።

ለሰባት ዓመታት የዘለቀው የሰላም እጦት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿን ለሞት በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ደግሞ ለስደት የዳረገባት ሶሪያ ከቦምብ ዝናብና ከጥይት እሩምታ ነፃ ሆና ሰላም የምትሆነውም በዚህ ዓመት ነው። ለአገሪቱ ሰላም መሆን ዋነኛ ምክንያት  የፖለቲካ መፍትሄ እንደሚሆን ያስቀመጠው ዘገባው፤ ከዚህ በተጓዳኝ፤ የአይ ኤስ አይ ኤስ የሽብር ቡድን በቀደሙት ዓመታት በኢራቅና በሶሪያ የነበረው ካሊፌት ማጣቱና ህልውናውም ከመነሳት ይልቅ ለመሞት የቀረበ መሆኑ ለአገሪቱ ሰላም መሆን ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር አብራርቷል።

 በተለይ በወታደራዊ አቅም ግንባታ ረገድ አሜሪካና አፍሪካ ፍቅራቸው የሚታደስበት ዓመት እንደሚሆን የተጠቆመ ሲሆን፤ የሳውዲው መሪ ማህማድ ቤን ስልማን የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ  ለውጥ ይበልጥ የሚያስቀጥሉበት እንደሚሆንም ተገምቷል፡፡

ሳውዲ አረቢያ በተለይ ከኢራን ጋር በገባችው ቁርሾ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከእስራኤል ጋር በፍቅር የምትከንፍበት ዓመት እንደሚሆን ያመላከተው ዘገባው፣ «ይህ መቼም ሊሆን አይችልም  የምትሉ ከሆነም ባለፈው ዓመት የኢራን እንቅስቃሴ በሚመለከት ሁለቱ አገራት የደህንነት መረጃ ልውውጥ ማድረጋቸውንና የሳውዲው መሪ እስራኤልን እንዲጎበኙ ከቤንያሚን ኔታኒያሁ አስተዳደር ጥሪ እንደቀርበላቸው ማስታወስ ብቻ ምስክር ይሆናችኋል»ብሏል።

ዓመቱ በየመን ያለው ሰብዓዊ ቀውስ ይበልጡኑ አስከፊ ገፅታ የሚላበስበት ይሆናል። በተለይ የቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አሊ አብደላ ሳላህ ድንገተኛ ግድያ የሰላም ድርድሩ ቦታ እንዳይኖረውና ቂም በቀል ያረገዘ ቀውስ እንዲፋፋም ያደርጋል። ሳውዲ አረቢያም በየመን ሰማይ በቦምብ ማዝነቧን ትቀጥላለች።

የአይ ኤስ አይ ኤስ የሽብር ቡድን አባላት በኢራቅና ሶሪያ ምድር የነበራቸው የበላይነት ካባ ቢገፈፍም፤ ቡድኑ ሞቱ ቢቃረብም የአልሞት ባይ ተጋድሎ በማሳየት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያደርሳቸውን የሽብር ጥቃቶቹን በዚህም ዓመት የሚቀጥል ሲሆን፣ አውሮፓን መሰረት ያደሩ ጥቃቶቹም ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚወስዱ ተገምቷል።

ዓለማችን ባሳለፍነው ዓመት የልዕለ ኃያሏን አገር ፕሬዚዳንት ጨምሮ የፈረንሳይና የደቡብ ኮሪያ መሪዎችን ቀይራ አሳይታናለች። ዘንድሮም ቢሆን አንዳንድ መሪዎቿን ለመቀያር አሊያም በሥልጣን ለማቆየት የምርጫ ሁነቶችን ትጠባበቃለች። ብራዚል ሜክሲኮ ጣሊያን እንዲሁም የራውል ካስተሮን የመሪነት አገልግሎት የበቃት የሚመስለው ኩባ ለምርጫ ሁነቶች ከሚሰናዱ አገራት ግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ።

ይህ ዓመት የአገራት ብቻም ሳይሆን የዓለማችን የፖለቲካ ምህዳርና ቀጣይ አቅጣጫ  የሚወስኑ ምርጫዎች የሚካሄዱበትም ነው። እንደ ሲቢሲ የዜና አውታር አበይት ጉዳዮች ተንታኝ ክሪስ ኦርፊዳ ትንተና፤ በተለይ በሩሲያ የሚካሄደው ምርጫ ሁነኛ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሌሉበትና ለይስሙላ የሚካሄድ በመሆኑ የብላድሚር ፑቲን ዳግም አሸናፊነትን ሳይታለም የተፈታ አድርጎታል። ሩሲያውያንም ቢሆኑ ለሚወዱት መሪያቸው ድምፃቸውን ለመስጠት የምርጫዋን ቀን በጉጉት ይጠባበቃሉ እንጂ ሌላ ተፎካካሪ ፓርቲን አሊያም ግለሰብን አይናፍቁም።

ቀደም ባሉት ዓመታት ፆታዊ ትንኮሳን ጨምሮ በተለያዩ ቀውሶች ስማቸው ቢብጠለጠልም በጣሊያን ፖለቲካ ምህዳር ላይ ገናና ስም ያላቸው ሰርቪዮ በርልስኮኒ ዘንድሮ በጣሊያን በሚካሄደው ምርጫ የፎርርዛ ጣሊያን ፓርቲ መሪ ሆነው ብቅ ይላሉ። በርካታ ወገኖች ከወቅቱ የአሜሪካን ፐሬዚዳንት ጋር የሚያመሳስሏቸውና ከታክስ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ጣሊያንን በበላይናት ከመምራት የፖለቲካ ስልጣን የተገለሉት የበርልስኮኒ ፓርቲም፤ ከዴሞክራቲክ ፓርቲው ማቲኦ ራንዚ ጋር በምርጫው ፍልሚያ ሜዳ ይተናነቃል።

ለሶስት አስርት ዓመታት አገሪቱን ያስተዳደሩት ሆስኒ ሙባረክ ከስልጣን መገርሰስ ወዲህ ላለፉት ስድስት ዓመታት ውጥረት ውስጥ የቆየችውና በአብዱል ፍታ አልሲሲ ዘመነ ስልጣን አንፃራዊ መረጋጋት የሰፈነባት ግብፅ፤ በዚህ ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ ከአልሲሲ ጋር የመቀጠል አሊያም የመለያየት ፍላጎቷን ታሳብቃለች።

ከአሜሪካና ከመሪዋ ጋር የመሰረቱት ወዳጅነት ክፉ ቀን ቢመጣም ማምለጫ ይሆናቸዋል በሚል የሚነገርላቸው አብዱል ፈታህ አልሲሲ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አገሪቱን የሚፈታተናትና በሻርማልሼክ ሪዞርትና፤ በኮፕቲክና ክርስቲያንና በሱፊ ሙስሊም ቤተ ሃይማኖቶች ላይ የደረሰው የሽብር ጥቃት ዳግም እንዳይከሰት በማስቆም ረገድ ህዝባቸው ከእርሳቸው ብዙ ይጠብቃል።

በዚህ ዓመት በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫም በቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙባረክ በትረ ስልጣን ዘመን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር የነበሩት አህመድ ሻፊክ የአል ሲሲ ቀንደኛ ተፎካካሪ  እንደሚሆኑ ይጠበቃል። ይሁንና ሰውየው በአሁኑ ወቅት ኑሮአቸውን በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ማድረጋቸውን ተከተሎ ወደ አገራቸው ተመልስው በምርጫ  እንዲወዳደሩ የአልሲሲ መንግስት አስተዳደር ፈቃድ ስለ መስጠት አለመስጠቱ ማንም እርግጠኛ አልተገኘም።

እንደ አልጀዚራው ብራንቤይ ፊሊብስ ትንበያ፤ የመካከለኛው ምስራቅ ትንቅንቅ ይበልጥ የሚጦፈውም በዚህ ዓመት ነው። በተለይ የመን፤ ሶሪያ እንዲሁም ሊባኖስ ደግሞ የቀውሱ ገፈጥ ቀማሽ  ሆነው ይቀጥላል። በተለይ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል ዋና ከተማ እየሩሳሌም ናት በሚል እውቅና መስጠታቸውን ተከትሎ የተቀሰቀሱ ውጥረቶች ይበልጡኑ ይሞቃሉ። የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ትሪሳ ሜይ በብሪክስ ድርድር ይበልጡኑ አቅምና አቋማቸው የሚፈትሸው በዚህ ዓመት ነው።

የዓለማችን ፖለቲካ ከተለያዩ ውስጣዊ እሰጣ ገባና መጠላለፎች እንዲሁም የጥርጣሬ እይታዎች ትዕይንት በተጓዳኝ፤ በተለያዩ ዘመን አማራጭ የቴክኖሎጂ ጥቃቶች የሚፈተንበት እንደሚሆን የሚያትቱም  በርካታ ወገኖች ሆነዋል።

በዚህ ረገድ የቻይና ሲጂቲኤን ዘገባ እንዳመላከተው ከሆነም፤ ዓለማችን በዚህ ዓመት ከባድ ፈተናና የፖለቲካ ስንክሳር ይጋረጥባታል። በተለይ የሳይበር ጥቃት የዓለማችን ትልቅ ራስ ምታት ይሆናል፤ በርካታ አገራትም ራሳቸውን ከጥቃቱ ለመከላከል አሊያም ለማምለጥ ሲራወጡ ይስተዋላል።

ምንም እንኳን በአሜሪካና በኮሪያ መሪዎች መካከል የተከፈተው የቃል ማስፈራሪያ ወደ ወታደራዊ ጦርነት የመቀየሩ ነገር እርግጥ ባይሆንም፤ አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ የሚያደርጉት ወታደራዊ ልምምድ ፒዮንግ ያንግን ክፉኛ ማስቆጣቱም አይቀሬ ነው።

በዓለማችን የጂኦፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ትንታኔና ግምቶችን በማስቀመጥ የሚታወቀው ካርትዝ በበኩሉ፤በዚህ ወር አጋማሽ የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ አዲስ የፖለቲካ አመራሮችን እንደሚሾሙና ዓመቱም ቻይናውያን ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸውንና አስተዋፆአቸውን የሚያጠናክሩበት እንደሚሆን ግምቱን አስቀምጧል። «የአገሪቱ መሪ ዢ ጂንፒንግ የዓለም አቀፋዊነት መሪ ሆነውና ሚናቸው ጎልብቶ የሚታይበት ይሆናል» ነው ያለው።

     የሰሜን ኮሪያ፣ የታይዋን እንዲሁም የደቡባዊ ቻይና ባህር ለቤጂንግ መንግሥት ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሚሆኑና በፍቅርና በጥላቻ መካከል በሚዋዝቀው የአሜሪካ ጉዳይም በቤጂንግ በኩል፤ዝቅተኛ ትኩረት የሚሰጠው እንደማይሆን አትቷል።

ወደ ፕሬዚዳንትነት መንበረ ስልጣኑ ከመጡ አንድ ዓመት ሳይሞላቸው ከአፍሪካ ጋር በፍቅር የወደቁት የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ማኑኤል ማክሮን ከአፍሪካ ጋር የጀመሩትን አፍላ ፍቅር ለማስቀጠል ሲውተረተሩ የሚታዩበት ዓመትም  እንደሚሆን ጠቁሟል። አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወደ አፍሪካ ለአራት ጊዜያት የተመላለሱት ማርኮን፤ አፍሪካን ለመለወጥ የሰጡትን ቃል ወደ ተግባር ለመለወጥም የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም ነው»ያለው።

የዶናልድ ትራምፕን የልዕለ  ኃያሏ አገር መሪነት እንዲሁም ብሪታኒያን ከአውሮፓ ህብረት እንደምትፋታ የተነበየውና ብዙ ጊዜ ትንቢት ከሚመስለው ምልከታው ጋር የሚያስፈራና አልፎ አልፎም የሚያሳዝነው  ክሬግ ሃሚልተን ፓርከር በበኩሉ፤ ይህ ዓመት ዓለማችን በፖለቲካ ምስቅልቅል የምትፈተንበት፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ምድራችን አይታቸው የማታውቃቸው ከባድ አደጋዎች የሚከሰቱበት እንደሚሆን ግምቱን አስቀምጧል።  የሰሜን ኮሪያ ፕሬዚዳንት ኪም ጆንኡን በህዝባዊ የተቃውሞ ለውጥ ከስልጣን እንደሚለቁና ከአገራቸው ተሰደው ቻይናን መሸሸጊያቸው እንደሚያደርጉ የገመተው ብዙዎችን አስደምሟል፤ አነጋገሯልም።

በርካታና ጠንካራ ተቃውሞዎች ቢሰነዘርባቸውም የቬንዙዌላው ፕሬዚዳንት፤ ኒኮላስ ማዱሮ በስልጣን መቆየት፣ ከ16 ዓመት በኋላ ፍፃሜው የሚጠበቀው የጆሴፍ ካቢላና በዴሞክራቲክ ኮንጎ ምርጫ፤ የአገሬውን ህዝብ ጨምሮ በርካታ ወገኖችን ያስደመመው የዚምባቤው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ከስልጣን መገርሰስና ቀጣይ የአገሪቱ ምርጫ፤ የካታሎን ከስፔን እንፋታ ጥያቄ ወደ መለያየቱ ማዘንበል ግምት የተሰጠባቸው ሌሎች አበይት የዓለማችን የፖለቲካ ጉዳዮች ሆነዋል።

ታምራት ተስፋዬ

Published in ዓለም አቀፍ

በአዲስ አበባ ከአምባሳደር ወደ ስታዲየም በሚወስደው መንገድ በእግር ሲጓዙ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ ክስተት ያጋጥሞታል፡፡ ይህ  ክስተት ብሔራዊ ቴአትር አካባቢም ይስተዋላል ይባላል፡፡ ለነገሩ መንገዱ ይለያይ እንጂ ድርጊቱ በበርካታ የከተማዋ አካባቢዎች ይፈጸማል፡፡

በዚህ አካባቢ ሲጓዙ ወጣቶች ምንዛሬ ይፈልጋሉ የሚል ጥያቄ እያነሱ ይከተለዎታል፡፡መልስ ሳይሰጡ ቢጓዙም አንዱን ወጣት ሲያልፉ ሌላው ይከተሎታል፡፡ ምንዛሬ ይፈልጋሉ የሚል ጥያቄ አሁንም ይቀርብሎታል፡፡ እነዚህ ፈንጠር ፈንጠር ብለው መንገዱ ዳር የቆሙ እንዲሁም መንገደኛ የሚመስሉ ወጣቶች አላፊ አግዳሚውን እየተጠጉ በሹክሹክታም አይደለም ድምጻቸውን ከፍ አርገው በገሀድ ጥያቄውን ያቀርባሉ፡፡ ምን እግር አመጣኝ እስኪሉ ድረስ ይጠየቃሉ፡፡

 ወጣቶቹ ይህን ጥያቄ በአደባባይ እና በጠራራ ፀሐይ ማንሳታቸው ያለመከሰስ መብት ያላቸው ያስመስላቸዋል፡፡ በዚህ ጥቁር ገበያ ሳቢያ በዶላር አዘዋዋሪዎች ላይ በተለያዩ ወቅቶች የተወሰደው እርምጃ ማንም ተመልሶ ወደ እዚህ ተግባር እንዲገባ የማያደርግና አስተማሪ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ይህን የሚያውቅ የማንትስን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም ባለ ነበር፤ አሁን ይህ ሁሉ ተረስቶ ይህን ያህል የሚያነጋግር የጥቁር ገበያ ግብይት ተስፋፍቷል፡፡

የወጣቶቹን ጥያቄ ሰምተን እንዳልሰማ የምናልፍ ብንኖርም በዚህ ግብይት ተጠቃሚ መሆን የሚፈልጉ ወገኖች ግን ወጣቶቹን ይከተሏቸዋል፡፡ በተለይም የዶላር ምንዛሬው ማሻቀቡን ተከትሎ እነዚህ ሰዎች ሥራቸውን እያጧጧፉ  የውጭ ምንዛሪ ፈላጊዎች ቁጥር እየጨመረና የሚያገኙት ኮሚሽን እያደገ መምጣቱም ይነገራል፡፡

እነዚህ ወጣቶች ደላሎች ናቸው እንጂ በራሳቸው መንዛሪዎች አይደሉም፤ ምንዛሬው የሚካሄደው በተለያዩ መደብሮች ውስጥ በስውር ነው፡፡ የአልባሳት፣ የሸጣሸቀጥና ሌሎች መደብሮች ህልውና የተመሠረተውም በውጭ ምንዛሪ ጥቁር ገበያ መሆኑም ይነገራል፡፡ መደብሮቹ በውትወታ የተካኑትን እነዚህን ወጣቶች በጥቂት ኮሚሽን የህገወጥ ድርጊታቸው ተባባሪዎች አድርገዋቸዋል፡፡

ከእነዚህ በተጨማሪ በውጭ ሀገር ግንኙነት ያላቸው የተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች የውጭ ምንዛሬውን ባሉበት ሀገር እየተቀበሉ ለኢትዮጵያውያን በብር ገንዘብ የሚሰጡም አሉ፡፡እነዚህ ምንአልባት ጥቂት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ብዙ ሀብት የሚያንቀሳቅሱ ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች ምንም ዓይነት የገንዘብ ለውውጥ ሰነድ አይሰጡም፤ ሥራው የሚሰራው በስልክና በመተማመን ነው፡፡

እንደሚታወቀው፤ የውጭ ምንዛሬ በተለያዩ መንገዶች ይገኛል፡፡ ሀገሮች የውጭ ምንዛሬን ወደ ውጭ ከሚልኩት ምርት፣ ከሚሰጡት አገልግሎት፣ ከተለያዩ ሀገሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት በብድርና እርዳታ ያገኛሉ፡፡ ይህ የውጭ ምንዛሬ በቀጥታ ለመንግሥት የሚደርስ በመሆኑም የእነዚህ የውጭ ምንዛሬ ቀበኞች መክበሪያ አይሆንም፡፡

እንደሚታወቀው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ የወጪ ምርቶች ላይ በትኩረት ይሰራል፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ፣ የግብርና ምርቶችን በመጠንና በዓይነት ለማሳደግ እንዲሁም በምርቶቹ ላይ እሴት በመጨመር ወደ ውጪ ለመላክ የሚከናወነው ተግባር ግቡ ለልማት የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማሳደግ ነው፡፡ በተለያዩ መንገዶች በብድርና እርዳታ የሚገኝ የውጭ ምንዛሬንም ለማሳደግ የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች ይሰራሉ፡፡

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ሀገራቸው በውጭ ምንዛሬ ይልካሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ባህር ማዶ ሆነው መደበኛው አገልግሎት በአቅራቢያቸው ባለመኖሩ ወይም አገልግሎቱን ባለማመናቸው ሳቢያ ገንዘብ በሰው ሊልኩ ይችላሉ፡፡ ይህ መንገድ ቀልጣፋ አገልግሎት ሆኖም አግኝተውት ሊሆን ይችላል፡፡ በርካታ ገንዘብ በአንድ ጊዜ ወይም በተደጋጋሚ በህጋዊ መንገድ መላክም የሚኖሩበት ሀገር ህግም ላይፈቅድ ይችላል፡፡ በዚህ የተነሳም በሰዎች መላክን ሊመርጡ ይችላሉ፡፡ ከዚህ በመለስ ደግሞ በጥቁር ገበያ ያለው ዋጋ የሚያስገኘው ጥቅም ታሳቢ የሚደረግበት ሁኔታ ሌላው ዋና ምክንያት ነው፡፡

ከዚህ የውጭ ምንዛሬ ውስጥ ባንኮች የተወሰነውን ያገኛሉ፡፡ ሌሎች ዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶችም እንዲሁ ከባንኮች ጋር ባደረጉት ትስስር አማካኝነት የተወሰነውን ገንዘብ ያገኛሉ፡፡ ባንኮቹ በቀጥታ ለእነሱ ተልኮ ወይም በተለይ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማበረታታት በሚል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዘረጉት የማበረታቻ ስርዓት ተጠቃሚ ለመሆን በሚፈልጉ ግለሰቦች የውጭ ምንዛሬ ግኝታቸውን እያሳደጉም ይገኛሉ፡፡ ከዚህ የተረፈው ግን በጥቁር ገበያ በኩል ነው የሚመነዘረው፡፡

ገንዘቡ በየትኛውም መንገድ ሀገር ውስጥ ይግባ የሚመነዘርበት መንገድ ግን ህግንና ህግን በተከተለ መንገድ መሆን ይኖርበታል፡፡ በሀገራችን የሚስተዋለው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው፡፡

ሀገር ለተለያየ የልማት ተግባር የውጭ ምንዛሬ በከፍተኛ ሁኔታ በምትፈልግበት በአሁኑ ወቅት ይህ ውድ ሀብት የቀበኞች መክበሪያ እንዴት ሊሆን ቻለ፡፡ ህብረተሰቡስ ይህን የግብይት መንገድ ለምን ሊመርጥ ቻለ የሚለው ሊመለስ የሚገባው ጥያቄ ነው፡፡

አሁን በአገራችን የባንኮች የውጭ ምንዛሬና የጥቁር ገበያው ዋጋ ያን ያህል የተጋነነ ልዩነት ያለው አይደለም፤ ይሁንና ግን ብዙ ገንዘብ የሚመነዘር ከሆነ ተጠቃሚነቱ እንዳለ አያጠራጥርም፡፡ ብዙዎች በአገልግሎቱ እየተሳቡ መሆናቸውም ይህንኑ ያመለክታል።

ይህ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለም በተለይም በውጭ ምንዛሪ ተገዝተው የሚመጡ ለልማታችን ለኑሯን በእጅጉ አስፈላጊ በሆኑት ሸቀጦች፣ ነዳጅ፣ ሰንዴ፣ ዘይትና ሌሎችም ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ  እንደሚያሳድር መገንዘብ ያስፈልጋል። በአሁኑ ወቅትም ጥቁር ገበያ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እየጎዳ ስለመሆኑ እየተነገረም ነው፡፡ ታዲያ ይህንን በዘላቂነት መቆጣጠር ያልተቻለው ለምን ይሆን?የቁጥጥሩ ሥራ ጊዜ እየጠበቁና እያደቡ ብቻ የሚከናወንስ መሆን አለበት ወይ?

በጥቁር ገበያ የሚካሄደው የውጭ ምንዛሬ ግብይት በመደበኛው አገልግሎት በባንኮች በኩል ብቻ እንዲካሄድ ቢደረግ በሀገሪቱ የሚታየውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በተወሰነ መልኩ ከመፍታቱም በላይ  ሕገወጥ በሆነው ጥቁር ገበያ ሊደርሱ የሚችሉ ችግሮችን መፍታት ይቻላል፡፡

በእርግጥ ባንኮች በውጭ ምንዛሬ ግብይት ውስጥ በስፋት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በባንኮች  የውጭ ምንዛሬ ግብይት የሚያካሂዱ ወገኖችን ለማበረታት የሎቶሪ ሽያጭም እያደረጉ ናቸው፡፡በቀጣይም ይህን ሥራቸውን በተጠናከረ መልኩ የሚያካሂዱበት ምቹ ሁኔታም ሊፈጥርላቸው ይገባል፡፡

በተለይም በአገሪቱ የገንዘብ ዝውውር ውስጥ ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉትን  እንደ ዌስተርን ዩኒየን፣ ደሀብሽል፣ ትራንስፋስትና ሌሎቸንም በተገቢው ሁኔታ ማስተዋወቅ ቢቻል፤ ባህር ማዶ ያሉትም ኢትዮጵያውያን በመደበኛው የባንክ አሰራር ገንዘባቸውን በመላክ አገራቸውንም ዘመዶቻቸውንም መጥቀም ቢችሉ የሚል ሀሳብም አለኝ፡፡

ምንም እንኳ ጥቁር ገበያ ቢኖርም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የባንክ ተጠቃሚ መሆናቸው ለመደበኛው አሠራር አመቺ ሁኔታን ቢፈጥርም ባንኮች ባለው የዋጋ ልዩነት ከጥቁር ገበያ ጋር መወዳደር አይችሉም፡፡ የየዕለቱን የውጭ ምንዛሪ ተመን የሚያወጣላቸው  ብሔራዊ ባንክ ነው፡፡  ባንኩ ያወጣውን ተመን መተላለፍ ደግሞ  ሕገወጥ ነው፡፡ በመሆኑም የባንኮችን የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ የሚያደርጉትን ጥረት ለማሳደግም  ጥቁር ገበያውን የመከላከል ዋንኛ ኃላፊነት የብሄራዊ ባንክና የሕግ አስከባሪው ይሆናል፡፡

እንደሚታወቀው የኢኮኖሚ እድገቱን ተከትሎ የውጭ ምንዛሬ ፍላጎቱ እየጨመረ ነው፡፡ሀገሪቱ አሁን ካለባት የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት አንጻር ሲታይ ለተለያየ የልማት ሥራዋ የሚያስፈልጋትን ግብአት ከውጭ ለማምጣት፣ ለፍጆታ እቃዎች ወዘተ፣ የውጭ ምንዛሬ በከፍተኛ መጠን ያስፈልጋታል።

በዚህ ላይ ለትምህርት፣ ለሥራ፣ ለንግድ፣ ለህክምና ይሁን ለሌሎች ጉዳዮች ወደተለያዩ የዓለም አገራት የሚጓዙ ሰዎች ጥቁር ገበያውን ይጎበኛሉ፡፡ በተለይ የንግድ ሥራው በጣም ጦፏል፡፡ ዱባይና ቻይና የሚመላለሰው ነጋዴ ቁጥር ስፍር የለውም፡፡ ሁሉም የውጭ ምንዛሬ ይፈልጋል፡፡ ለዚህ ሁሉ ከመንግሥት የሚገኝ የውጭ ምንዛሬ የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ቢኖርም በቂ ላይሆን ይችላል፡፡ ይህም ለጥቁር ገበያው መስፋፋት አንድ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡

መንግሥት የኢኮኖሚ እድገቱ እና የውጭ ግንኙነቱ ያስከተለውን ይህን እንቅስቃሴ ለመደገፍ እንዲያስችል እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች የውጭ ምንዛሬ በህጋዊ መንገድ የሚያገኙበት ሁኔታ ማመቻቸትም ይኖርበታል፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ጥቁር ገበያውን የሚፈለገውን ያህል መቆጣጠር አዳጋች ከመሆኑም በተጨማሪ የእነዚህን ወገኖች እንቅስቃሴ መገደብም ይሆናል፡፡

ከዚህ በተረፈ አንድ አገር ወደ ውጭ የምታልከው ምርት እና የምትሰጠው አገልግሎት እያደገ ሲመጣ እና የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ እየጨመረ ይመጣል፡፡ ወደ ሀገር ውስጥ ከምታስገባው ምርትና አገልግሎት የምታስወጣው ምርትና አገልግሎት እየጨመረ ሲመጣም እነዚህን ምርቶችና አገልግሎቶች ለማስገባት ስትል የምታስወጣው የውጭ ምንዛሬ እየቀነሰ ስለሚመጣም የንግድ ሚዛኑም ወደ ሌሎች ሀገሮች ከማጋደል ይወጣል፡፡ ይህን ተከትሎ የውጭ ምንዛሬ ችግሩ እየተቀረፈ ሊመጣ ይችላል፡፡

እንዲያም ሆኖ የውጭ ምንዛሬ ለማግኝት በትኩረት የሚሰራ ከመሆኑም በተጨማሪ የሚያዘውም በጥንቃቄ ነው፡፡ በበለጸገውም ሀገር ይሁን በሌላ የውጭ ምንዛሬውን በከንቱ የሚዘራ የለም፡፡ በውጭ ምንዛሬ ላይ የሚደረግ ህገወጥ ግብይት እና ዝውውር ሀገርን በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳል፡፡ ገንዘቡ ለሀገር ልማት መዋል ሲገባው ቅድሚያ ለማይሰጣቸው ተግባሮች አልፎም ተርፎ ለህገወጥ ተግባሮች ሊውል ስለሚችልም ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ የግድ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በጥቁር ገበያው ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ሊጠብቅና ምንዛሬው ትክክለኛውን መንገድ ይዞ እንዲጓዝ ማድረግ ይገባል፡፡

በእምነት

Published in አጀንዳ

ለውጥ ተግባር ነው የሚል ብሂልና አስተሳሰብ ቢኖርም ያለአስተሳሰብ አንድነት ተግባር አይኖርም የሚለው አባባልም እውነታነቱ የጐላ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ተግባር ለመከወን መነሻ መሆን የሚገባው በሚተገበረው ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ አቋም መያዝና በአንድ አቅጣጫ መጓዝ ነው፡፡ ይኼም ደግሞ ያለ አስተሳሰብ አንድነት ዕውን ሊሆን ከቶውኑ አይችልም ፡፡

ይኼንን ጉዳይ ዛሬ ለማንሳት የፈለግነው ከሰሞኑ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጉባዔ ጋር ተያይዞ የአስተሳሰብ አንድነት ለመፍጠር እየተወሰደ ያለውን ጊዜ ትክክለኝነት አጽንኦት ለመስጠት ነው፡፡ ብዙዎች ሁሌም ከድርጅቱ ስብሰባ በኋላ «የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የትምክህትና የጠባብነት አዝማሚያ ድርጅቱንም ሆነ ሀገር በመምራቱ ሂደት እንቅፋት ፈጥሮብኛል የሚለው የመግለጫ አካል የነጠላ ዜማ ያህል የተለመደ የኢህአዴግ መዝሙር ሆኗል፤ የሚፈለገው ተግባር ነው» ሲሉ ይደመጣሉ፡፡

ትክክል ነው። ተግባር ሁልጊዜም አስፈላጊ ጉዳይ ነው። ሁሌም ችግሮቼ እኒህ እኒህ ናቸው ብሎ እየደጋገሙ መኖሩ አሰልቺ ከመሆኑም አልፎ ትልቅ ሀገርን የመምራት ኃላፊነት ለተጣለበት ድርጅት ይኸ ጉዳይ የሚፈጥረው ተግዳሮት ትልቅ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ስለዚህ ተግባር፣ ተግባር ተግባር… የሚለው የህዝብ ጥያቄ ተገቢና ተቀባይነት ያለው እንዲሁም በፍጥነት ሊመለስ የሚገባው ጉዳይም ነው፡፡

ይሁንና እዚህ ላይ ቆም ብሎ ሊታሰብ የሚገባው ጉዳይ ጠባብነት፣ ትምክህት፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ እርስበርስ መጠራጠር ወዘተ የአስተሳሰብ በሽታዎች ስለሆኑ ሊፈቱ የሚችሉት የተዛነፈ አስተሳሰብን በማከም ብቻ መሆኑ ነው። የተዛነፈ አስተሳሰብ የሚታከመው ደግሞ ጊዜ ወስዶና ቁጭ ብሎ በመነጋገርና የአስተሳሰብ አንድነት በመፍጠር ነው፡፡ ስለሆነም ኢህአዴግ የገጠሙትን ችግሮች ዘርዝሮ ለመፍትሄውም እንዲህ ጊዜ ሰጥቶ መገምገሙ ይበል ሊያሰኘው እንጂ ጊዜ እንዳባከነ ተደርጎ ሊቆጠርበት አይገባም። 

ኢህአዴግ የአራት ብሄራዊ ድርጅቶች ጥምረት ቢሆንም በትጥቅ ትግሉም ሆነ በጸረ ድህነት ትግሉ እጅግ አስደማሚ ድሎችን እያስመዘገበ እዚህ የደረሰው ከተግባር በፊት ረዘም ያለ ጊዜ ወስዶ በተግባሩ ግብ፣ በአቅጣጫውና በሚያጋጥሙት ችግሮች አፈታት ዙሪያ የአስተሳሰብ አንድነት ፈጥሮ መንቀሳቀስ በመቻሉ ነው፡፡ ድርጅቱ የሚወግንለት የኅብረተሰብ ክፍል ስላለና ልማታዊ አስተሳሰብን ስለሚያራምድ ጉዞዎቹ በፈተና የተሞሉና ውጣ ውረድ የበዛባቸው ነበሩ፡፡ በገነባው ሠራዊት ከአፍሪካ አገሮች ቀዳሚ የተባለውን የደርግ ሠራዊት ጨምሮ ለዘመናት የተከማቸው ድህነትን አፍርሶ የበርካታ ድሎች ባለቤት የመሆኑ ሚስጥርም ከምንም ነገር ቅድሚያ የአስተሳሰብ አንድነት ለመፍጠር ጊዜ መስጠቱና በውይይትና በንግግር አምኖ ተግባራዊ እርምጃ መውሰዱ ነው፡፡

ኢህአዴግና በእሱ ጥላ ስር ያሉ ድርጅቶች ገና ከውልደታቸው በ1968፣ በ1973፣ በ1977  እንዲሁም በ1993 ዓ.ም እና አሁንም የገጠማቸውን የአስተሳሰብ መለያየት የቀረፉት ሰከን ብለው በመቀመጥ፣ ችግሮችን አንድ በአንድ ነቅሰው በማውጣት፣ የአስተሳሰብ አንድነት ፈጥረውና ችግሮችን መፍቻ የጋራ መንገድ ቀይሰው መንቀሳቀስ በመቻላቸው ነው፡፡ አሁንም እየደገሙ ያሉት ይኸንኑ ነው፡፡

ስለሆነም ተግባር ተግባር ተግባር እያለ እየጠየቀ ያለው ህዝብ ኢህአዴግ አሁንም እያደረገ ያለው የህዝብ ጥያቄ የሆነውን ተግባር ለመፈፀም ጊዜ ወስዶ እየሠራና የአስተሳሰብ አንድነት እየፈጠረ መሆኑን ነው፡፡ ይህንን አድርጐም እንደ ከዚህ በፊቱ በችግር ውስጥ ነጥሮና ጠንክሮ እንደሚወጣ ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል፡፡

የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እንደ ሁልጊዜው ከታኅሳስ 3 እስከ 20/2010 ዓ.ም ድረስ ጊዜ ወስዶና ቁጭ ብሎ የአስተሳሰብ አንድነቱን የሸረሸሩበትን ውጤታማነቱን የቀነሱበትንና የህዝብ አመኔታው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የፈጠሩበትን ጉዳዮች ነቅሶ አውጥቷል፡፡ ለተፈጠሩት ችግሮች ጣቱን ማንም ላይ ሳይቀስር የሥራ አስፈጻሚው ችግር እንደሆነና ለዚህም ኃላፊነቱን ራሱ እንደሚወስድ ጥርት ባለ ቋንቋ አስቀምጧል። በዚህ ብቻም ሳይታጠር ከዚህ ችግር ለመውጣት የሚጓዝበትን አቅጣጫም አንጥሮ አስቀምጧል፡፡ ይኸም ለቀጣይ ለሚተገብራቸው ተግባራት በጥሩ ቁመና ላይ እንዲገኝ ትልቅ አቅም እንደሚሆነው ይታመናል፡፡ ችግርን ማወቅ የመፍትሄ ግማሽ መንገድ ነው እንደሚባለውም አሁን ያከናወነው ተግባር የህዝብን ጥያቄ በብቃት በመመለስ ታሪክ መስራቱን እንዲቀጥልና አምኖ የስልጣን መንበሩን ያስረከበውን ህዝብ እንዲክስ አስተማማኝ አቅም ይሆነዋል፡፡

በአጠቃላይ በግራም ሆነ በቀኝ አሁን ኢህአዴግ ያለው ምርጫ አንድና አንድ ብቻ ነው፡ ይሄውም እንደከዚህ ቀደሙ በዓላማ ጽናት የአስተሳሰብ አንድነቱን አጠንክሮና ወገቡን አጥብቆ የሀገርን ሰላምና ድህንነት ማረጋገጥ! ከቀደምት ታሪኩ በመነሳትም ይህንን በተሳካ ሁኔታ እንደሚፈጽመውም ይታመናል!

Published in ርዕሰ አንቀፅ

አዲስ አበባ፦ የሰመራ ዩኒቨርሲቲ 22 ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን  ለአካባቢው ማህበረሰብ ማቅረቡን አስታወቀ፡፡ 

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ መሐመድ አህመድ ኢብራሂም በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት ፤ዩንቨርሲቲው ከመማር መስተማር ጎን ለጎን የአካባቢውን አርብቶና ከፊል አርብቶ አደር ማህበረሰብ ችግር የሚፈቱ ጥናትና ምርምሮችን ማካሄድና አገልግሎት መስጠት ተልዕኮው በመሆኑ ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

በዚህም ማህበረሰቡ የዘመናዊ መስኖ ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ፣ ሥራ አጥ ወጣቶች በንብ ማነብ ራሳቸውን እና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ ለማስቻል የሚረዱ ምርምሮችን በማካሄድ  ለማህበረሰቡ ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡

 ምርምሮቹም በዋናነት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶችን የሚያግዙ ናቸው ያሉት አቶ መሐመድ፣ በክልሉ ያሉትን ወንዞች በመጠቀምም በዓመት አንዴ ብቻ ያመርቱ የነበሩትን  ከፊል አርብቶ አደሮች  በዓመት ሦስት ጊዜ እንዲያመርቱ ማስቻሉን  አስታውቀዋል፡፡

እንደ አቶ መሐመድ ማብራሪያ፤ ዩኒቨርሲቲው ባለፈው የትምህርት ዘመንም አርባ ዘጠኝ ችግር ፈቺ ምርምሮችን አካሂዷል፤ በተገኘው ውጤት ላይ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ውይይት በማድረግ በቀጣይ ሁለት ወራት ለህብረተሰቡ ያቀርባል፡፡

በተያዘው የትምህርት ዘመን 45 ጥናትና ምርምር ሥራዎችን ለመሥራት መታቀዱን የሚናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ከዚህ ውስጥም የአካባቢውን ወጣቶች በእንጨት ሥራዎች ላይ ለማሳተፍ የሚጠቅም ጥናት በዚህ ዓመት ይካሄዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በ2022 በአርብቶና ከፊል አርብቶ አደር ማህበረሰብ ልማት በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የመሆን ራዕይ ያነገበ በመሆኑ ይህንን እውን ለማድረግ እያደረገ ያለውን ያለሰለሰ ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

መላኩ ኤሮሴ

 

Published in አጀንዳ

ከጊዮን ሆቴል ፊት ለፊት ያለው ሜዳ እንደወትሮው ተሸከርካሪዎች አልቆሙበትም፤ ሌጣውንም አይደለም፡፡ የተለያዩ ቀለማት ያላቸው ድንኳኖች ተጥለውበታል፡፡ ሞቅ ያለ የባህል ሙዚቃ ድምጽ እያስተገባ ለአካባቢው ልዩ ድምቀት ሰጥቶታል። የፌዴራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ያዘጋጀው የ2010  በጀት ዓመት አንደኛ ዙር ሀገር አቀፍ የሞዴል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽንና ባዛርን ማስተናገድ ጀምሯል።

በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ላይም ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞቹ ያመረቷቸውን የተለያዩ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ አልባሳት ፣ ቅመማ ቅመሞችና ምግብ ነክ ሸቀጦችን በተዘጋጀላቸው ስፍራ  ይዘው ቀርበዋል፡፡ የእለቱ የክብር አንግዶችና የሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም የከተማዋ ነዋሪዎችም እየተዘዋወሩ ምርቶቹን እየጎበኙ ሲሆን፣ ያሻቸውንም እየሸመቱ ናቸው ።

ወይዘሮ አጸደ ተክሌ ከትግራይ ክልል በመምጣት የማር ጠጅን እንዲሁም የራሳቸው የፈጠራ ውጤት የታከለባቸውን የተለያየ ጣዕም ያላቸውን የአበሻ አረቁ አይነቶች ይዘው ቀርበዋል።

ወይዘሮ አጸደ እንደሚሉት ፤ስራውን የጀመሩት በ 500 መቶ ብር የመነሻ ካፒታል ቢሆንም አሁን ለ 17  ሰዎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል፤ ባለሀብት በመሆንም ለአገራቸው ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡

ወይዘሮ አጸደ በተለያዩ ባዛሮችና ኤግዚቢሽኖች ተሳትፈዋል፡፡ ከክልላቸው አልፈው በአዲስ አበባ፣ ሀዋሳ፣ አሰላና ሌሎች ቦታዎች ላይም እየተጋበዙ ባዛር በማሳየት  ደንበኞችንም አፍርተዋል፡፡ በዚህም የገበያ ትስስር ለመፍጠር እና ከሌሎች ልምድ ለመቅሰም ችለዋል፡፡  በተለይ አገር አቀፍ ባዛርና ኤግዚቢሽን ጥቅሙ ከፍተኛ መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ አጸደ፣ከዚህ በፊት በተካፈሉባቸው ተመሳሳይ ባዛሮች አማካይነትም በመላው አገሪቱ  ታዋቂ ለመሆን በቅተዋል፤ ከፍተኛ ገቢም ለማግኘት ችለዋል፡፡

መሰል ኤግዚቢሽንና ባዛሮች መንግስት በማመቻቸት ዘርፉን በማሳደግ የገበያ ትስስርና የልምድ ልውውጥ እንዲኖር  ማድረጉ የሚደነቅና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበትም መሆኑን ተናግረዋል።

ወይዘሮ አይናለም ገዛኸኝ የድሬዳዋ ነዋሪ ናቸው፡፡ በተለያዩ ኤግዚቢሽንና ባዛሮች ላይ መሳተፋቸው በሌሎች ክልሎች ከሚገኙ መሰሎቻቸው ልምድ እንዲቀስሙ እና የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ አስችሏቸዋል፡፡

ባዛሮቹና ኤግዚቢሸኖቹ በሀረር፣ በሰመራ፣ አዲስ አበባና ሌሎች ክልሎች ላይ ደንበኞችን እንዲያፈሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን ፣በተለያዩ ጊዜያት ወደ እነዚህ አካባቢዎች እየሄዱ ባዛር በማሳየት ምርቶቻውን ልከው በመሸጥም ተጠቃሚ በመሆን ላይ እንደሚገኙ ያብራራሉ።

በቆዳና የቆዳ ውጤቶች ምርት ላይ የተሰማራችው ወይዘሪት ገዳምነሽ አዳሙ ባዛሮችና ኤግዚቢሽኖች ምርትን ለማስተዋወቅ፣ ለመሸጥ፣ ደንበኛ ለማፍራት እንዲሁም ከሌሎች ልምድ ለመቅሰም ሚናቸው  በቀላሉ የሚታይ አይደለም ትላለች።

በዓመት ለአንድ ወይም ለሁለት ጊዜ ብቻ በሚዘጋጁ ኤግዚቢሽንና ባዛሮች ላይ የተፈጠረ የገበያ ትስስር ብቻውን ኢንተርፕራይዞቹን ከፍ የማድረግ አቅም አይኖረውም የምትለው ወይዘሪት ገዳምነሽ፣የማሳያ ቦታ በየአካባቢው እንደሚቻችም ትጠይቃለች። 

የፌደራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አሰፋ ፈረደ እንዳሉት፤ ክልሎችና ከተሞች ከሚያዘጋጇቸው ኤግዚቢሽንና ባዛሮች በተጨማሪ ሀገር አቀፍ የኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽንና ባዛር በማካሄድ የምርትና አገልግሎት ሀገራዊ የገበያ ትስሰር ፣ የተሞክሮ ልውወጥ እና የማስተዋወቅ የአሰራር ሥርዓት ተዘርግቶ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።

በዚህ አሰራርም  በ2009 ዓ.ም  በአገር አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛሮች አማካይነት ስምንት ክልሎችንና ሁለት የከተማ አስተዳደሮችን ተሳታፊ በማድረግ 505 ኢንተርፕራይዞች ምርትና አገልግሎታቸውን የመሸጥና የማስተዋወቅ ስራ ተሰርቷል፡፡ በዚህም የ9 ነጥብ 36  ሚሊዮን ብር ሽያጭና የገበያ ትስስር ተፈጥሮ ከ 62 ሺ በላይ ኢንተርፕራይዞችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመትም ኢንተርፕራይዞቹ ምርትና አገልግሎታቸውን እንዲያስተዋውቁ የገበያ ትስስርና ሽያጭን እንዲፈጽሙ ለማድረግ መታቀዱን አቶ አሰፋ ገልጸው፣ በዚህም ኢንተርፕራይዞቹ ከተጠቃሚው ጋር በቀጥታ በሚያደርጉት  ግንኙነት ዘላቂ የገበያ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።

በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ላይም 185 ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችና ከማኑፋክቸሪግ ዘርፍ ውጭ የሚገኙ አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች፣ 7 አነስተኛና መካከለኛ ኢንደስትሪዎች  በድምሩ 192 ኢንተርፕራይዞች ተሳታፊ እንደሚሆኑም የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

 

ዜና ሀተታ

እፀገነት አክሊሉ

 

 

 

    

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።