Items filtered by date: Wednesday, 03 January 2018

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ አንዴ የሚሞቀው ሌላ ጊዜ የሚረግበው የኢትዮጵያና የግብፅ  ጉዳይ ሰሞኑን ደግሞ የሞቀ የመወያያ ርእስ ሆኗል፡፡ የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በአዲስ አበባ ላይ ባደረጉት ውይይት ግብፅ፤ ‹‹በአባይ ጉዳይ ላይ የዓለም ባንክ ያደራድረን ›› የሚል ሃሳብ ይዛ ቀርባለች፡፡ በአንጻሩ ኢትዮጵያ ደግሞ ጉዳዩን ላጢነው የሚል  ምላሽ ሰጥታለች፡፡ ምሁራን ደግሞ በሦስተኛ ወገን አማካኝነት እንደራደር የሚለውን ሃሳብ  ህጋዊ መሰረት የሌለው፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ የማይሄድ ነው ሲሉ የግብፅን ሃሳብ ውድቅ አድርገዋል።

በግድቡ ግንባታ ዙሪያ ግብፅ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ በጋራ የሚያጠኗቸው ጥናቶች አሉ፡፡ የእነዚህ ጥናቶች የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት እንኳን ገና ይፋ ሳይሆንና ውይይቱም ሳይቋጭ በግብፅ በኩል የሚሰጡት መግለጫዎች የቴክኒክ ኮሚቴው ውይይት አብቅቶለታል የሚል አቋም የያዙ ይመስላል የሚሉት በናይል የትብብር መድረክ (ናይል ቢዝን ኢንሼቲቭ) የምሥራቅ ናይል የቴክኒክ አህጉራዊ ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ  አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ ናቸው። የቴክኒክ ውይይቱን ግብፆች እንዲቀጥል ባይፈልጉም በኢትዮጵና በሱዳን በኩል በውይይት የሚፈታ ጉዳይ ነው የሚል አቋም መኖሩንም ይገልጻሉ፡፡

ለዚህ ሃሳብ ማጠናከሪያቸው ደግሞ በቅርቡ የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ አዲስ አበባ በመጡበት ጊዜ አዲስ ሃሳብ ይዘው እንደመጡ ነው የሚናገሩት፡፡ «ይህ አዲስ ሃሳብ  በውይይቱ (በድርድሩ)  ሂደት ሦስተኛ አካል  ይሳተፍ የሚል ነው፡፡ ሦስተኛ አካል  እናሳትፍ ብቻ ሳይሆን የሦስተኛውን አካል ማንነት ጭምር ራሳቸው ወስነው የዓለም ባንክ ይሁን ነው የሚሉት፡፡ ይህ የሚያመላክተው የቴክኒክ ሂደቱ በእነሱ በኩል እንዳበቃለትና ጉዳዩን ፖለቲካዊ አንድምታ ብሎም ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው ለማድረግ ግብ ይዘው መንቀሳቀስ መጀመራቸውን ነው። ግብፆች ይህን ቢሉም የቴክኒክ ውይይቱ አልቆለታል ወይንስ አላለቀለትም የሚለው በሦስቱ አገራት ስምምነት የሚወሰን ነው የሚሆነው። ሦስተኛ አካል ይሳተፍ ወይስ አይሳተፍ የሚለውንም  ሦስቱ አገራት በጋራ ሆነው ነው መወሰን ያለባቸው» ባይ ናቸው አቶ ፈቅ፡፡

እንደ አቶ ፈቅ ማብራሪያም፤ ሦስተኛ አካል ያስፈልጋል? የሚለውንም  አገራቱ በጋራ የሚወስኑት እንጂ በተናጠል የሚወሰን ጉዳይ አይደለም፡፡ ሦስተኛ አካል የሚያስፈልገው የቴክኒክ ሂደቱ  ሲያበቃለት እንጂ በሂደት ላይ እያለ አይደለም፡፡ አበቃለት ቢባል እንኳን ኢትዮጵያና ሱዳን ሦስተኛ አካል ስለማስፈለግ ገና አልተስማሙም፡፡ የወሰን ተሻጋሪ ውሃ አጠቃቀምን በተመለከተ ጉዳዩ በአገራቱ ቢያዝ ነው የሚመረጠው፡፡ ምክንያቱም አገራቱ  በውሃው አማካኝነት ተሳስረዋልና ነው፡፡ አንዱ አገር የሌላውን ፍላጎትና ስጋት ያውቃል፡፡ ምንም እንኳ ፍጥጫ ቢፈጠርና አለመተማመን ቢኖርም አገራቱ የተሳሰሩበት ገመድ አለ፡፡ የአገራቱን ፍላጎት፣ ስጋት፣ አንድነትና እርስ በእርሳቸው መረዳዳታቸውን ሦስተኛው አካል አይጋራውም፡፡ በዚህ ሳቢያ ሦስተኛው አካል ሂደቱን ሊያበላሸው ይችላል። ቢቻል ቢቻል አገራቱ በራሳቸው መካከል ያለውን ልዩነት ቁጭ ብለው ተነጋግረው በትዕግስት ቢፈቱት ይመረጣል፡፡

‹‹ግብፅ የቴክኒክ ሂደቱ አያዋጣኝም፡፡ ከዚህ በኋላ ለውጥ አያመጣም የሚል ፍራቻ ካላት በሦስትዮሽ ውይይቱ ላይ ሦስተኛ አካል እናሳትፍ የሚል ሃሳብ አቅርባ  ከሁለቱ አገራት ጋር መወያየት ነበረባት፡፡ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ ሦስተኛ አካል እናሳትፍ ብለው የሚስማሙ ከሆነ እንኳን የሦስተኛው አካል የሥራ ኃላፊነቱና ሚናው ምንድነው፣ ፍትሐዊነቱ፣ ገለልተኛነቱና በዚህ ዙሪያ ያለው  ልምድ መታየት አለበት፡፡ እንዲሁም በተለይ ወንዙን በተመለከተ ለላይኛውና ለታችኛው የተፋሰስ አካባቢዎች  ፍትሐዊ የሆነ ፖሊሲ አለ ወይ የሚለው በጥልቀት መታወቅ አለበት እንጂ አንድ አገር ተነስቶ ይህ ይሁን ብሎ መምረጥና መወሰን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለመደ አሠራር አይደለም ›› የሚል አስተያየት አላቸው፡፡

የአገራቱ  ውሳኔ ሆኖ ሦስተኛ አካል ይግባ የሚሉም ከሆነ፤ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ለሦስተኛ ወገን  የኃላፊነት ወሰንና ሚና ተሰጥቶት የቴክኒክ ሃሳብ በማቅረብ ማሳተፍ ይቻላል። ውሳኔ ሰጭ አካል  ከሆነ ግን ምን አልባት ግጭቱን ሊያባብሰው ይችላል የሚል ስጋት በአቶ ፈቅ ዘንድ አለ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት የዓለም አቀፍ ህግ መምህር የሆኑት ዶክተር ደረጀ ዘለቀ በበኩላቸው፤ ድርድር በህግ ማዕቀፍ ውስጥ ባለ ግንኙነት የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት ከሚወሰዱ አማራጮች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ድርድር ማለት በሁለቱ ወይም በሦስቱ አገሮች መካከል በህግ ማዕቀፍ ውስጥ አለመግባባት አለ ከሚል ነው የሚነሳው፡፡ ምክንያቱም እንደራደር ሲባል  በሁለት ወገኖች መካከል ህጋዊ ጥያቄ የሚያስነሳ የመብት ጥሰት እንዳለ ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ስለዚህ ድርድር የሚኖረው ህጋዊ ግጭት ሲኖር ነው፡፡ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ደግሞ የህዳሴውን ግድብ አስመልክቶ የህግ ጥሰት ወይም በህጋዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስገድድ አንዳች የጋራ የህግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ ድርድር  የሚለው የግብፅ ሃሳብ ‹‹ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ነው›› ሲሉ ይነቅፉታል፡፡

አደራዳሪው ማን ይሁን ወደ ሚለው ከገባን የህግ ጥሰት  አለ የሚለውን እንደ መቀበል ይቆጠራል የሚሉት ዶክተር ደረጀ፤ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ  የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ አድርገናል፤ መረጃም እየተለዋወጥን ነው፡፡ ይህን የምናደርገው ከበጎ ፈቃድና ለዲፕሎማሲ ግንኙነት ሲባል እንጂ አንዳችም ይህን የማድረግ የህግ ግዴታ የለብንም፡፡ ከዚህ አኳያ ግብፅ የናይል ተፋሰስ አገሮች የትብብር ማዕቀፍ ፈራሚ ብትሆን ኖሮ በዚህ  የህግ ማዕቀፍ መሰረት የህግ ግዴታ ስላለብን እንወያይ ካልተስማማን እንደራደር ማለት ይችሉ ነበር፡፡ ሆኖም ማንኛውንም የዓለም አቀፍ የህግ ማዕቀፍ አልቀበልም ብሎ የቆየ መንግሥት ስለድርድር ሊያወራ አይችልም፡፡ ከአጥር  ውጪ ቆይቶ እንደራደር የሚባል ነገር የለም፡፡ እናም ይላሉ ዶክተሩ፤ እነሱን ተከትሎ ድርድሩ  ውስጥ መግባት የእነሱ ወጥመድ ሰለባ መሆን ነው ይላሉ፡፡

 ግብፅ የዓለም ባንክን ለምን መረጠች ?

አቶ ፈቅ ‹‹የግብፅ የዓለም ባንክ ያደራድረን» የሚለው ሃሳብ  እንግዳ እንዳልሆነና ከዚህም በፊት ተመሳሳይ ሃሳብ አቅርበው ነበር ይላሉ። «ከአሁን በፊት እኤእ በ2013 እና በ2014 የሚኒስትሮች ውይይት በነበረበት ወቅት ግብፅ ይህን ሃሳብ አቅርባ ሦስተኛ  አካል አናሳትፍም፡፡ ይህ የሦስታችን ጉዳይ ነው ብለው  ኢትዮጵያና ሱዳን ውድቅ አድርገው ባታል፡፡ ግብፅ ይህን ጉዳይ አሁንም እንደገና ማንሳቷ ምን አልባት ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው ገና ለገና አውቀው ኢትዮጵያን ለመክሰስ ሌላ መንገድ ለመክፈት ሊሆን ይችላል» ሲሉም ይገልጻሉ፡፡

ምንም እንኳ የቴክኒክ ሂደቱ ስለመጓተቱ ትልቁን ኃላፊነት መውሰድ ያለባቸው ግብፆች ቢሆኑም ሂደቱ ስለተጓተተ ያንን ለማፋጠን ይረዳል የሚል በጎ አመለካከት ኑሯቸውም ሊሆን ይችላል ይህንን ሃሳብ ያቀረቡት፡፡ አሊያም ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ከፍተኛ ድጋፍና ብድር እያገኘች ያለች አገር ናት፡፡ የሦስተኛ አካል ተሳትፎን ኢትዮጵያ የማትቀበል ከሆነ ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻከር  አስበውም ሊሆን ይችላል የሚል እምነት በአቶ ፈቅ ዘንድ አለ፡፡

ሦስተኛ አካል ማሳተፍን የመጀመሪያ አማራጭ ከማድረግ ይልቅ በአሁኑ ጊዜ የቴክኒክ ጥናቱ እየተካሄደ ስለሆነ ሂደቱ በተቻለ ፍጥነት የሚሄድበትን ሁኔታ ማመቻቸት ቢቻል የተሻለ ይሆናል፡፡  አገራቱ በዚህ ሂደት መተማመን ባልቻሉበት ሁኔታ ሦስተኛ አካል ማምጣት ያለመተማመኑን ያጠናክራል እንጂ መፍትሄ ይሆናል የሚል እምነት እንደሌላቸውም ነው አቶ ፈቅ የገለጹት፡፡

ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ብድርና ዕርዳታ የምታገኝ አገር ናት፡፡ ግብፆችም ይህንን ስለሚያውቁ በዓለም ባንክ ጡንቻ የእነሱን ፍላጎት ማስፈጸም ነው ዓላማቸው የሚል አመለካከት በዶክተር  ደረጀም ዘንድ አለ።  ኢትዮጵያ ለልማት  ብድር የምታገኝባ ቸውን በሮች መዝጋት የግብፅ ብሄራዊ ስትራቴጂ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ለዓብነትም የጣና በለስ የኃይል ማመንጫ ግንባታ በ1999 ዓ.ም ሲጀመር  ኢትዮጵያ ብድሩን ከአፍሪካ ልማት ባንክ እንዳታገኝ ያደረገችው ግብፅ ናት፡፡ ስለዚህ የዓለም ባንክን ወደ ጨዋታው የሚያስገቡት አንደኛ የልማት ፋይናንስ ምንጮችን ለማድረቅና  በዓለም ባንክ ጡንቻ ኢትዮጵያን ለመጠምዘዝ ነው፡፡

‹‹ግብፅ የሦስትዮሽ ውይይቱን የሁለትዮሽ ለማድረግ ነው የምትጥረው፡፡ ይህ ደግሞ አዲስ አይደለም፡፡ እኤእ በ 20014 እና በ2015ም  በነበሩት ውይይቶች ግብፅ ኢትዮጵያን ሱዳንን ትተን ሁለታችን ብቻ እንወያይ የሚል ሃሳብ አንስታለች፡፡ በወቅቱም  ኢትዮጵያ  ሃሳቡን ውድቅ ያደረገችው ጉዳዩ የሦስትዮሽ እንጂ የሁለታችን ብቻ አይደለም በሚል ነው» ይላሉ ዶክተር ደረጀ፡፡ ግብፆች ይህንን የሚያደርጉበትን ዋና ምክንያት ሲያብራሩም በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያና በሱዳን  መካከል ያለው ግንኙነት ከምንጊዜውም በላይ የተጠናከረበትና ሰፊ ይዘት ያለው ሆኗል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ  በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ በግብፅና በሱዳን መካከል ግንኙነቱ እየቀዘቀዘ የመጣበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በአብዛኛው  ግብፆች ከሱዳን ጋር ያለን ግንኙነት የተበላሸው ሱዳን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ለኢትዮጵያ ድጋፍ ስለሰጠች ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡ ለዚህ ምነው ሱዳንን ወደ ጎን ትተን ሁለታችን እንነጋጋር የሚሉት።

ቀጣይ ፈተናዎች

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ቀጣይ ፈተናዎችን በተመለከተ አቶ ፈቅ እንዳሉት፤ በአገራቱ መካከል ያለመስማማት ሊፈጠር የሚችለው ግድቡ ውሃ መያዝ ሲጀምር ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ከግብፅ የሚሰማው መግለጫ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አሞላል ላይ ከእኛ ጋር ካልተስማማ በስተቀር ግድቡን መሙላት አይችልም የሚል ነው።  በአንጻሩ በኢትዮጵያ በኩል ጥናቱ ተጠናቆ የግድቡ አሞላልና የውሃ አለቃቀቅ ላይ  ሦስታችንም ከተስማማን ተስማማን፤ ሳንስማማ የመሙያው ጊዜ ከደረሰ ግን እንሞላለን የሚል አቋም ነው ያለው፡፡ በዚህ ጊዜ የተወሰነ አለመግባባትና ወይንም የቃላት እሰጣ ገባ ሊፈጠር ይችላል እንጂ ግድቡ አንዴ ውሃ ከያዘና ኃይል ማማንጨት ከጀመረ  በኋላ ግን ግንኙነቱ ሊሻሻል ይችላል ባይ ናቸው፡፡

ዶክተር ደረጀ ደግሞ፤ ግብፅ በዓለም አቀፍ ህግና ግንኙነት የሚታወቁ እርምጃዎችን ነው እየወሰደች ያለችው፡፡ ጨቋኝና ኢፍትሐዊ የውሃ አጠቃቀምን እስከተቻላት ድረስ አራዝማ ማቆየት አልያም ወደ ፍትሐዊ የውሃ ክፍፍል የሚመጣበትን ጊዜ በተቻለ መጠን ማዘግየት ከተቻለም ማስቀረት ነው ዓላማዋ፡፡ ለዚህ ነው በተጠና መልኩ  በየጊዜው የተለያዩ ካርዶቿን የምትመዘው፡፡ ስለዚህ ምንም የሚፈጠር ነገር የለም፡፡ አሁን ባለው የአቋም ልዩነት ምክንያት አለመግባባት ሊኖር ይችላል፡፡ ሆኖም እነዚህ አለመግባባቶች በዲፖሎማሲ ይፈታሉ የሚል እምነት አላቸው፡፡

ግድቡ ሲጠናቀቅ እስኪሞላ ድረስ ፍሰቱን ሊያዛባ ይችላል እንጂ ፍሰቱ አይቀንስም፡፡ ለእነሱም ያልተከፈለበት ከፍተኛ ጥቅም ያገኛሉ፡፡ እንዲያውም ግድቡ የመስኖ ቦዮቻቸውና ግድቦቻቸው ሲሞሉባቸው ደለሉን ለማውጣት በብዙ ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ያወጡ የነበረበትን አጋጣሚ  ያስቀርላቸዋል፡፡

ምክረ ሃሳብ

‹‹ የዓለም ባንክ ያደራድረን የሚለውን የግብፅ ሃሳብ ያስፈልጋል ወይንስ አያስፈልግም የሚለውን በጥናት ተንትኖና ከተለያዩ አቅጣጫዎች አይቶ መወሰን አለበት» የሚሉት አቶ ፈቅ የዓለም ባንክ ለአገሮች ብድር የሚሰጥበት ፖሊሲ  ውስጥ 705 የሚባል ነገር አለ፡፡ በዚህ ፖሊሲ  አንቀጽ ላይ የወሰን ተሻጋሪ ወንዝን በተመለከተ አገራት ለልማት ብድር ሲጠይቁ የተፋሰሱን አገራት ይሁንታ ይጠይቃል፡፡  በዚህ ምክንያት  የዓለም ባንክ ፖሊሲ ፍትሐዊ አይደለም፡፡ ያ ማለት ግን በፖሊሲው ብቻ ዓለም ባንክ ፍትሐዊ ነው ወይንም ኢፍትሐዊ አይደለም ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ ሌሎች መታየት ያለባቸው ጉዳዮችም አሉ ነው የሚሉት አቶ ፈቅ፡፡

በሦስቱ አገራት መካከል ውሃን በተመለከተ የሚደረገው የቴክኒክ ውይይት በቴክኒክ ባለሙያዎች ነው የሚመራው፡፡ የወሰን ተሻጋሪ ውሃ በሦስት ደረጃ ሊመራ ይችላል፡፡ የመጀመሪያው የቴክኒክ ደረጃ ነው፡፡ በአገራቱ መካከል የሚኖረው ግንኙነት የውሃን ጉዳይ በሚመለከተው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ባለሙያዎች የሚመራ ይሆናል፡፡ በውሃ ዙሪያ የሚኖረውን እጥረትና ፍጥጫ በቴክኒክ መፍታት ይቻላል፡፡  ችግሩ አገራቶቹ ቁጭ ብለው ተነጋግረው የውሃውን ፍስት የሚጨምሩበትና ብክለቱን የሚቀንሱበት ሁኔታ ለመፈጠር ስላልፈለጉ እንጂ  ያለውን የውሃ እጥረት በቴክኒክ መፍታት ይቻላል፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን ኢትዮጵያ የናይል ጉዳይ ወደ ቴክኒክ እንዲመለስ ማድረግ አለባት፡፡

በቴክኒክ መፍታት ካልተቻለ ግን ወደ ፖለቲካ ይሄዳል፡፡ ጉዳዩ ፖለቲካ ደረጃ ከደረሰ በአብዛኛው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው የሚመራው፡፡ የፖለቲካ ውይይት ደግሞ እኛን አያዋጣንም፡፡ ምክንያቱም የፖለቲካ ውይይት መስጠትና መቀበልን የሚጠይቅ ስለሆነ ከዚህ በኋላ ደግሞ እኛ የምንሰጠውም የምንቀበለውም ነገር የለም፡፡

በፖለቲካ ደረጃ ሊመራ ካልቻለ ደግሞ ወደ ደህንነት ነው የሚሄደው፡፡ ይህ ደግሞ አገራቱ ፍጥጫ ውስጥ ገብተዋል ማለት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግብፆች ውሃውን በፖለቲካና በደህንነት መካከል ነው አንጠልጥለውት የሚገኙት፡፡ እኛንም ወደ ፖለቲካ እንድንወስደው እየገፉን ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ወደ ፖለቲካና ደህንነት እንዳይሄድና በቴክኒክ ደረጃ እንዲቋጭ ጥረት ማድረግ ነው የሚጠበቅባት ሲሉ ምክረ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል አቶ ፈቅ፡፡

ኢትዮጵያ ግጭት በሌለበት መደራደር የሚባል ነገር የለም ብላ ምላሽ መስጠት አለባት የሚሉት ዶክተር ደረጀም፤ ሆኖም በግብፅ ጨዋታ ተጎትታ የምትሳተፍ ከሆነ ውጤቱ አሳዛኝ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ አቋም «እስከ ዛሬ  ድረስ ስናደርግ የነበረውም  የቴክኒክ ውይይት በበጎ ፈቃድ ለዲፕሎ ማሲያዊ ግንኙነት ሲባል እንጂ የህግ ግዴታ የለብንም የሚል መሆን አለበት» ሲሉ ነው ምክረ ሃሳባቸውን የሰጡት፡፡

ጌትነት ምህረቴ

Published in ፖለቲካ

በኢትዮጵያ የባንክ ተጠቃሚዎች ቁጥር በጣም አነስተኛ የሚባል ነው፡፡ የባንኮች ቴክኖሎጂ አጠቃቀምም ውስን ነው፡፡ ባንኮች ቴክሎጂን በመጠቀም የሚሰጧቸው የኢንተርኔት፣ የኤ ቲ ኤም፣ የሞባይልና የፖስ ማሽን አገልግሎቶችም እርስ በእርስ የተሳሰሩ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ባንኮቹ በቴክኖሎጂ በደንብ ዘምነው ለህብረተሰቡ የተሟላ የባንክ አገልግሎት የመስጠት ደረጃ ላይ አልደረሱም የሚባለው፡፡

በባንኮች ዘመናዊ የክፍያ ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ ኢትስዎች አክሲዮን ማህበር 17 የንግድ ባንኮችን እርስ በእርስ የማስተሳሰር ሥራ እያከናወነ ይገኛል፡፡ ዘንድሮ የባንኮችን የሞባይል፣ የፖስና፤ የኢንተርኔት ቴክኖሎጂዎችን እርስ በርስ በማናበብ የተለያዩ የባንክ አገልግሎቶችን መስጠት ይጀመራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በእነዚህና በመሰል ጉዳዮች ዙሪያ ከኢትስዎች አክሲዮን ማህበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብዙነህ በቀለ ጋር ቆይታ አድርገናል፤ እነሆ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በኢትስዎች አማካኝነት የሚሰጡ የባንክ አገልግሎቶችን ቢገልጹልን?

አቶ ብዙነህ፡- በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎት ተደራሽነት ገና ውስን ነው፡፡ በዚህ በኩል ብዙ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የባንክን አቅም ገና አልተጠቀም ንበትም፡፡ ከዚህ አኳያ ከዚህ ቀደም በኢትስዎች አማካኝነት የሁሉንም ባንኮች የኤ ቲ ኤም አገልግሎቶችን እርስ በርስ አገናኝተናል፡፡ በዚህም በማንኛውም ባንክ ኤ ቲ ኤም  ካርድ በሁሉም ባንኮች ኤ ቲ ኤም ማሽኖች መጠቀም ተችሏል፡፡ አሁን ደግሞ የሚቀሩት የሞባይል፣የኢንተርኔትና የፖስ አገልግሎቶች ናቸው፡፡

ዘንድሮ የባንኮችን የሞባይል፣ የፖስና የኢንትርኔት ቴክኖሎጂዎችን እርስ በርስ በማናበብ  የተለያዩ የባንክ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡ ይህም የሞባይል፣ የኢንተርኔትና የፖስ አገልግሎት እየሰጡ ባሉት ባንኮች ነው ተግባራዊ የሚደረገው፡፡ በተለይ የሞባይል ባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ከ10 የማይበልጡ ባንኮችን እርስ በእርስ የማናበቡ ጥረት እየተሞከረ ነው፡፡ ሥራው እየተጠናቀቀ ስለሆነ አገልግሎቱ በቅርብ ጊዜ ይጀመራል  ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በቀጣይ ግን ሁሉም ባንኮች ይካተታሉ፡፡

ሌላው በዚህ ዓመት ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የሁሉንም ባንኮች ፖስ ማሽኖች በአንድ ካርድ መጠቀም የሚያስችለውን ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡ ይህ በአንድ ሆቴል ወይም ሱፐር ማርኬት ሁሉም ባንኮች ፖስ ማሽኖች ማሳቀመጥ ሳያስፈልጋቸው የአንዱ ለሌሎቹ ማገልገል ይችላል፡፡ የፖስ አገልግሎትን ተግባራዊ ለማድረግ የነጋዴዎች ፍላጎት ሊኖር ይገባል፡፡ ለተጠቃሚዎች የተለያዩ ማበረታቻዎችን ማድረግ አገልግሎቱን ለማስፋት ይረዳል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የባንኮቹ በዘመናዊ የክፍያ ስርዓት ውስጥ እርስ በርስ መተሳሰር  ለባንኮቹ፣ ለተጠቃሚውና ለኢኮኖሚው የሚያበረክተው አስተዋፅዖ ምንድን ነው ?

አቶ ብዙነህ፡- ባንኮቹ በዘመናዊ የክፍያ ስርዓት መተሳሰራቸው ለባንኮች ወጪ ቆጣቢ፣ ለደንበኞች አማራጮችን ያሰፋል፡፡ ደንበኞች ባሉበት ቦታ ሆነው በቀላሉ የባንክ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ ወደ ባንክ የሚገባው የገንዘብ መጠንም እያደገ እንዲሄድ ጉልህ አስተዋፅዖ ያበረክታል፡፡

በቴክኖሎጂ የመተሳሰሩና የመናበቡ ሥርዓት ገንዘብ ለማውጣት፣ ለማስገባት፣ ለማዘዋወርና ለመገበያየት ብቻ ሳይሆን የውሃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የታክስና  መሰል መንግሥታዊ ክፍያዎችን ለመፈጸም ያስችላል፡፡

 አብዛኛው ህዝብ በኤሌክትሮኒክስ ግብይት እንዲያካሂድ ስለሚጋብዝ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ በጣም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ምክንያቱም ገንዘቦች ሁሉ በባንክ ስርዓት ውስጥ እንዲያልፉ ያደርጋል፡፡ በዚህም ፕሮጅክቶችን ፋይናንስ ለማድረግ የሚያስችል ገንዘብ በባንኮች እንዲኖር ያስችላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- እርስ በእርስ በማስተሳሰሩ ፕሮጀክት  እነማን ይሳተፋሉ?

አቶ ብዙነህ፡- የባንኮችን የሞባይል፣ ፖስና የኢንተርኔት አገልግሎቶች እርስ በርስ በማስተሳሳሩ ሥራ ሁሉም ባንኮች ይሳተፉበታል፡፡ እነሱ ከእኛ ጋር አማካሪዎቻቸውን አሰማርተው ይሠራሉ፡፡ ምክንያቱም ከእኛና ከብሄራዊ ባንክ የመረጃ ስርዓት ጋር በአገሪቱ ያሉትን 17 የንግድ ባንኮች ጋር ተናባቢ ማድረግ ነው ዋና ሥራው፡፡ እነዚህ ሁሉ ባንኮችና  የቴክኖሎጂ አቅራቢዎቻቸው ጭምር ይሳተፋሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ የባንክ ስርዓት ውስጥ ምን ለውጥ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል?

አቶ ብዙነህ፡- በአገሪቱ የባንክ ስርዓት ላይ ስር ነቀል ለውጥ ያመጣል፡፡ ሌሎች አገሮች የእኛን ብሄራዊ የክፍያ ስርዓት እንደ ጥሩ ተሞክሮ በማየት እየመጡ ልምድ እየቀሰሙ ነው፡፡ ምክንያቱም በአንድ ዓመት ውስጥ ትልቅ ለውጥ አሳይተናል፡፡ ዘግይተን ወደ ስርዓቱ ስለገባን የሌሎቹን ጠንካራና ደካማ ጎን በመለየት የተሻለውን ስርዓት ነው የመረጥነው፡፡ ይህ እየተስፋፋ ሲሄድ በክፍያ ስርዓታችን ጥሩ ለውጥ ያመጣል፡፡ የጥሬ ገንዘብ ልውውጥ ቀርቶ ሁሉም ነገር በቴክኖሎጂ የሚፈጸም ይሆናል፡፡

በአገሪቱ ወጥ የሆነ ክፍያ ስርዓት መዘርጋት ሁለተኛው ሥራችን ነው፡፡ ሁለቱንም ጎን ለጎን እያስኬድን ነው ያለው፡፡ አንዱን እያጠናን ሌላኛውን እንተገብራለን፡፡ ምቹ ሽግግር በመፍጠር በመላ አገሪቱ የትኛውም ባንክና የፋይናንስ ተቋም በሞባይል፣ በፖስና በኢንተርኔት  እርስ በራሱ እንዲናበብ ይደረጋል፡፡ ስለዚህ በፋይናንስ ተደራሽነትና ቀልጣፋ አገልግሎት ዙርያ  ለውጥ በሚያመጡ ተግባራት ላይ በትኩረት እየሠራን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ባንኮችን እርስ በእርስ ለማስተሳሰር በሚደረገው ሥራ ምን ያህል ገንዘብ ወጪ ተደርጎበታል?

አቶ ብዙነህ፡- እስከአሁን 216 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎል፡፡ 80 በመቶ የሚሆነው ገንዘብ የዋለው ለመሰረተ ልማት ዝርጋታ ነው፡፡ ፖስ ፡የኤ ቲ ኤም ማሽንና የሞባይል ባንኪግ አገልግሎት መሰረተ ልማቶቹን የሚያሟሉት ባንኮቹ ናቸው፡፡ እኛ የምንሠራው የሁሉም ባንኮች የመሰረተ ልማቶች  እርስ በእርሳቸው ተናባቢ ማድረግ ነው፡፡ በእኛ ስርዓት የተካተቱ (ሲስተም የገቡ)ከባንኮቹ የኤ ቴ ኤም ማሽን በጨመሩ ቁጥር እርስ በእርስ ይተሳሰራሉ ማለት ነው፡፡ የኤ ቲ ኤም ቁጥር ባደገ ቁጥር ማንኛውም የባንክ ደንበኛ የትስስሩ ተጠቃሚ ይሆናል ማለት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ወጥ የክፍያ ስርዓት መዘርጋቱ በባንኮች ተወዳዳሪነት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖራል?

አቶ ብዙነህ፡- የመሰረተ ልማቱ ወጥ መሆን በተወዳ ዳሪነታቸው ላይ የሚያከትለው ተፅዕኖ የለም፡፡ መሰረተ ልማቱን በመጠቀም የየራሳቸውን አገልግሎት በመስጠት ሊፎካከሩ ይችላሉ፡፡ ውድድሩ መሰረተ ልማት ላይ አይደለም፡፡

አዲስ ዘመን፡- የባንኮች የኤ ቲ ኤም አገልግሎት በኢትስዎች አማካኝነት እርስ በእርስ በመተሳሰሩ ምን ያህል ገንዘብ ተላልፏል?

አቶ ብዙነህ፡- በአንድ ዓመት ውስጥ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ በኢትስዎች አማካኝነት ተላልፏል፡፡ በቀን በአማካይ 25 ሺ የባንክ ደንበኞች በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ስርዓቱ  ይጠቀማሉ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ብዙ መሥራት አለብን፡፡

አዲስ ዘመን፡- ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ባንኮችን እርስ በርስ በማናበቡ ሥራ እንደ ተግዳሮት የሚጠቀሱ ጉዳዮች ምንድን ናቸው?              

አቶ ብዙነህ፡- በትብብር የሚሠራ ሥራ የራሱ ውጣ ውረዶች ይኖሩታል፡፡ ሁሉንም ባንኮች ወደ አንድ ዓይነት አስተሳሳብ ለማምጣት ጊዜ ይወስዳል፡፡ የክፍያ ስርዓቱን ለማስተሳሳር በሚደረገው ሥራ ብሄራዊ ባንክ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡እያንዳንዱ ባንክ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ስለሚጠቀም ይህን የማስተሳሰር ሥራ አስቸጋሪ ነው፡፡ የቴክኖሎጂ አቅራቢዎች ጥቅም ማግኘት ይፈልጋሉ፡፡ እያንዳንዱ ባንክ ከራሱ ቴክኖሎጂ አቅራቢ ጋር የሚያደርገው ድርድርም ጊዜ የሚፈጅና አስቸጋሪ ነው፡፡

ስርዓቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ማድግ አለበት፡፡ የሰው ኃይሉም በቴክኖሎጂ አጠቃቀሙ አብሮ እየተሻሻለ መሄድ ይኖርበታል፡፡ ህብረተሰቡም ስለ ቴክኖሎጂው በቂ ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል፡፡ የኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓትን መጠቀም ያለውን ፋይዳ ለህዝቡ የማስረዳቱን ኃላፊነት በባለቤትነት የያዘው አካል የለም፡፡

የቅንጅት ጉድለትም በሥራው ላይ የራሱን አሉታዊ ተጸእኖ ፈጥሯል ማለት ይቻላል፡፡ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይልና የኔት ወርክ አገልግሎት መቆራረጥ ለዘመናዊ የክፍያ ስርዓቱ እንደ ተግዳሮት ይጠቀሳሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ምንድን ናቸው?

አቶ ብዙነህ፡- የትኩረት አቅጣጫችን በመላ አገሪቱ የክፋያ ስርዓቱ በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ታግዞ እንዲካሄድ ማድረግ ነው፡፡ ባንኮች ብቻ ሳይሆኑ ማንኛውም የፋይናንስ ተቋም እርስ በርስ ተናበው ለህዝቡ ጥራቱን የጠበቀና ተደራሽ የሆነ የፋይናንስ አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ኢትስዎች የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ተግባራዊ እንዲሆን የበኩሉን ሚና እየተወጣ ይገኛል፡፡

ቀደም ብለው በተጠኑ ጥናቶች በኢትዮጵያ የፋይናንስ ሽፋኑ 22 በመቶ ነው፡፡ በፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ መሰረት 70 በመቶ ለማሳደግ ግብ ተይዟል፡፡ ለዚህ ግብ መሳካት ዋናው መሳሪያ ደግሞ በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ የክፍያ ስርዓት መዘርጋት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የኢትስዎች ተሳትፎ ትልቅ ሚና አለው፡፡

 ዜጎች በኤሌክትሮኒክስ ስርዓት በታገዘ መልኩ ቀልጣፋ የሆኑ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ  ለማድረግም እየተሠራ ነው፡፡ አገልግሎቱ ሲጀመር ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ይጨምራል፡፡ መልካም አስተዳደርን ከማስፈን ረገድም ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡

ለምሳሌ አንድ ሰው የመንግሥት መስሪያ ቤት ሄዶ አገልግሎት ሲያገኝ ለአገልግሎቱ የሚጠየቀው ክፍያ ሊኖር ይችላል፡፡ ይህን በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ሥርዓት መፈፀም ይችላል፡፡ ሥርዓቱ ደንበኛው የመንጃ ፈቃድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ፣ የውሃና መሰል መንግሥታዊ ክፍያዎች በቀላሉ በሞባይል ወይም በኢንተርኔት ባለበት ቦታ ሆኖ መክፈል ያስችለዋል፡፡

መንግሥት ለተጠቃሚው የሚከፍለው ካለም በዚሁ ስርዓት ማከናወን ይችላል፡፡ እነዚህን መንግሥታዊ አገልግሎቶች በሙሉ በብሄራዊ ክፍያ ስርዓት ስለሚተሳሰሩ ባሉበት ቦታ ሆነው መክፈል ይችላሉ፡፡ ኢትስዎች እነዚህን አገልግሎቶች ለማቀላጠፍ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ነው፡፡ አገልግሎቱም በዚህ ዓመት ይጀመራል፡፡

 የሞባይል ተደራሽነት በፋጥነት እያደገ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ 58 ሚሊዮን የሞባይል ተጠቃሚዎች አሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ ከ40 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት መደበኛ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህን ከባንክ አገልግሎት አንጻር ስናየው ሰፊ ነው፡፡ ይህን የሞባይል አገልግሎት በመጠቀም በኢትስዎች አማካኝነት ባንኮችን እርስ በእርስ በማስተሳሰር ደንበኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡

ይህ አገልግሎት ወጪ ቆጣቢ ከመሆኑም ባሻገር ተደራሽነትን ለማስፋት ያስችላል፡፡ ይህ የሞባይል አገልግሎት በደንበኞቻቸው ብቻ ተወስኖ የቆየውን አሠራር ለመቀየር ያስችላል፡፡ ይህን ለማስቻል የማናበብና የማስተሳሰር ሥራውን እየሠራን እንገኛለን፡፡ የሞባይል ባንክ አገልግሎት ስርዓት ያላቸው ባንኮች ደንበኞቻቸው ከአንዱ ባንክ ወደ ሌላው ባንክ ገንዘብ በማስተላለፍ አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ፡፡

ጌትነት ምህረቴ

Published in ኢኮኖሚ

ሐምሌ 9 ቀን 2011 ዓ.ም፡፡ ይህቺ ቀን ከ11 ሚሊዮን ለሚበልጡት ደቡብ ሱዳናውያን ልዩ ትርጉም አላት፡፡ የዘመናት ደም መፋሰስ የተቋጨባት፣ የአዲስ ንጋት ጮራ የፈነጠቀባት፣ ነፃነት የታወጀባት ታሪካዊ ቀናቸው ናት፡፡  አዲሲቷ ደቡብ ሱዳን 195ኛዋ አገር ሆና ዓለምን የተቀላቀለችበት፡፡ ለሃምሳ ዓመታት በተደረገ ትግል እ.ኤ.አ በሐምሌ ወር 2011 ነፃነቷን ተቀዳጀች። ይሄንኑ ተከትሎ ደቡብ ሱዳናዊያን ደስታቸውን በአደባባይ ገለጹ። አገሪቱን ራሷን የቻለች ሉአላዊ የመሆኗን እውነታ የተቀበሉት ከልባቸው፤እውነቱ የመረራቸው ደግሞ በስላቅ «ያድርግልሽ» ሲሉ መልካሙን ተመኙላት፡፡ ለአዲሲቷ አፍሪቃዊት አገር።

ደቡብ ሱዳን ለመምራት በተካሄደ ምርጫ ሳልቫ ኬር የፕሬዚዳንትነት መንበረ ስልጣኑን ተረከቡ፡፡ ዶክተር ሪክ ማቻር ደግሞ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን አዲሷን አፍሪካዊት አገር ለመምራት ቅንጅት ፈጠሩ። የተሻለች ደቡብ ሱዳንን የመፍጠር እቅድ ተይዞ ወደ ተግባር ተገባ። ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር ከተለያዩ አገራት ጋር ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በመፍጠር ጉዞውን ቀጠሉ።

በጁባ ምድር ለነፃነት በትብብር የተነሳው ክንድ ፤ለአገር ልማት በአንድነት መሰለፉ በቅብብሎሽ ተሰማ። የዕድገት ብልጭታን ለማምጣት ተስፋዎች ፈነጠቁ። በነዳጅ ሀብቷ የታደለችው ምድር ተፈጥሯዊ ሀብቷን በመጠቀም አገሪቷን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ፋኖው ተቀጣጠለ። ይህም ለሦስት ዓመታት ያህል ተጓዘ። ከዚህ በኋላ ግን ጉዞው እንደታሰበው አልቀጠለም፡፡ ያልተጠበቀ አውሎንፋስ ከወዲያ ወዲህ ያራግባት ጀመር፡፡

የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዴት በምክትላቸው ፕሬዚዳንት ሬክ ማቻር የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መደረጉ ተሰማ፡፡ ለሠላማዊው አየር መበከልም ምክንያት ሆነ፡፡ በድርጊቱ የተበሳጩት ሳልቫ ኬር ምክትላቸውን ከኃላፊነት አነሷቸው። በፕሬዚዳንታቸው ላይ ያሴሩት ሪክ ማቻር የከሸፈውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራቸውን ለማሳካት የመንገዳቸውን አቅጣጫ ቀየሩ፡፡ ከሳልቫኬር በተቃራኒ በመቆም አማጽያንን በማስታጠቅ ጦርነት አወጁባቸው።

ሰላም በነገሠባት በዚህች ምድር ላይ ከሦስት ዓመት በኋላ የመጀመሪያዋ የተኩስ ድምፅ ተሰማች። ከሱዳን ለመገንጠልና ነፃ ለመውጣት በአንድነት አብረው ለዘመናት ሲዋደቁ የኖሩ የደቡብ ሱዳን ጎሳዎች እርስ በርስ ጦር ለመማዘዝ ተዘጋጁ፡፡ ጎሳ ድንበር ሆኖ አይለያየንም ብለው አብረው ለመኖር የተስማሙ ደቡብ ሱዳናውያን፤ ጎራ ለይተው ሊታኮሱ፣ ጎሳ መድበው ሊጫረሱ፣ ዳግም ለሌላ ጦርነት ክተት አውጀው ተነሱ፡፡ የሁለቱ ዝሆኖች ግጭት ምናልባትም በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች መሰደድና ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆነ።

ደቡብ ሱዳናዊያን ለአራት ዓመታት ያህል ባደረጉት የእርስ በእርስ ጦርነት 100 ሺህ ያህል ሰዎች ወደ ሞት አምርተዋል፡፡ የመገዳደሉ ደረጃ መክረሩን ተከትሎም ከሀገሪቱ ዜጎች መካከል 1/3ኛው ከሚኖሩት ቀዬአቸው አንጻራዊ ሰላም ወዳለበት የአገሪቱ ክፍል ተጓዙ። ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከአገሪቱ ሙሉ ለሙሉ መልቀቁ ዋስትናዬ ነው በማለት እግራቸው ወደመራቸው ጎረቤት አገራት ተሰደዱ።

የእርስ በርስ ግጭቱ ከዜጎች መሰደድ በተጨማሪ የአገሪቱን ኢኮኖሚም ክፉኛ ጎድቷል፡፡  አሁን የዋጋ ግሽበቱ በአንድ ሺህ በመቶ መናሩ ነው የሚነገረው፡፡ የመንግሥት ሠራተኞችም ደመወዝ ከተከፈላቸው ዓመት እንዳለፋቸው ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕን ዋቢ አድርገው የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። የእርስ በዕርስ ጦርነቱ እንዲያበቃ የዓለም አገራት አሳሰቡ፡፡ ለዚህ ዕውን መሆን ደግሞ የሚመለከታቸው አካላት ጣልቃ ገብነት ወሳኝ እንደሆነ ተሰማ፡፡ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብና የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች ትኩረታቸውን ወደ ደቡብ ሱዳን አደረጉ። የእርስ በርስ ግጭቱ እንዲያበቃ ጩኸታቸውን አሰሙ። በጁባ የሠላም አየር እንዲሰፍን ጥሪ አቀረቡ፡፡

ቢቢሲ ከሰሞኑ በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያስችል ውይይት መደረጉን ተከትሎ ለአራት ዓመታት አኬልዳማ የሆነችው ደቡብ ሱዳን ወደ ሰላም እንደምትመጣ ጽፏል። የዕርስ በዕርስ ጦርነቱ እንዲቆም ባለፉት አራት ዓመታት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስከ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ጥረት ማድረጋቸውን ዘገባው አስታውሷል።

ወደ ሰላም የመምጣቱ ሁኔታ እውን ቢመስልም በየጊዜው መደፍረሱ ግን አልቀረም። በታጣቂ ኃይሎች የእርስ በዕርስ ብሎም በስልጣን ላይ ካለው መንግሥት ጋር የሚያደርጉት ውጊያ በየጊዜው እያገረሸ ዘልቋል። በዚህ መስመር ለአራት ዓመታት በመጓዝ ዛሬ ላይ የደረሰው የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ባለፈው የፈረንጆቹ ታኅሣሥ ወር 2017 መጨረሻ አካባቢ ሁለቱ ኃይሎችና ሌሎች በርካታ የታጠቁ ተቃዋሚ ኃይሎች በአዲስ አበባ ተገኝተዋል።

የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች ጦርነትን ለማቆም፣ የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ እና ለተጎዱት ሰብዓዊ ዕርዳታን ለማድረስ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙርያ  ከመግባባት መደረሱን ቢቢሲ በዘገባው አካቷል። በውይይቱ ላይ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ማህበራዊ ተቋማት እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሃሳብ እንዲካተት መደረጉን ጽፏል። በሃገሪቱ ሰላምን በማረጋገጥ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን እንግልት ለማስቆም የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የመደረስ እምነት ማሳደሩን ዘገባው አትቷል፡፡

ዘ ኢስት አፍሪካ ጋዜጣ ደግሞ፤ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ አንድ ሃሳብ ባይመጡ ኖሮ ቀጣዩ የደቡብ ሱዳን ሁኔታ ወደ ባሰ ችግር ያመራ እንደነበር በዘገባው አስፍሯል። ለዚህም አስገዳጅ እርምጃ ለመውሰድ ይጠብቁ ለነበሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፣ ለአውሮፓ ህብረት እና የአፍሪካ ህብረትን ሃሳብ ያስቀየረ ነው ተብለዋል፡፡

ዘገባው እንዳብራራው፤ በቀጣዩ የካቲት ወር 2018 ባለፈው ጊዜ ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጋር ያደረገችውን ምክክር የምትቀጥል ይሆናል። በፈረንጆቹ 2015 በአገሪቱ ሰላም ለማስፈን ከስምምነት ተደርሶ በነበረው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ትልቁ ትኩረቱ ይሆናል።

ከዚህ በተጨማሪም በመንግሥት መዋቅር እንዲሁም በሽግግር ጊዜ ደህንነት ሁኔታ ላይ ምክክሮች እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል። የሁለቱ ኃይሎች ቀጣይ ድርድር የሥልጣን ክፍፍል ቀመር መቅረፅና ምርጫ ማካሄድ ላይ የሚያጠነጥን እንደሆነ ተገልጿል።

ፕሬዚዳንት ሳልቫኬር የፈረንጆቹ 2018 አዲስ ዓመትን የመልካም ምኞታቸውን ለህዝባቸው ለመግለጽ ብቅ ባሉበት ወቅትም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ንግግራቸውን ማሰማታቸውን ነው ዘ ኢስት አፍሪካ ጨምሮ የገለጸው፡፡ አዲሱ ዓመት በአገሪቱ ሰላም የሚወርድበት ጊዜ ነው። መንግሥት ራሱን እንደ አዲስ በማዋቀር በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል። የተከፋፈለው ህዝብ ልዩነቱን አስወግዶ አንድነቱን ያጠናክራል፡፡ ‹‹ይህ ተግባራዊ እንደሚሆን ቃል እገባለሁ›› ሲሉ ተደምጧል።

ዶክተር ሪክ ማቻር በበኩላቸው ፤ ስምምነቱ  በፈረንጆቹ  2015 ተደርጎ የነበረው  ስምምነትን የሚከልስ ነው፡፡ ይሄንኑ ስምምነት መጠበቁ አገሪቱን ወደ ሰላም ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ላይ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው መናገራቸው በመረጃው ተጠቅሷል፡፡ ይሄም ሁኔታ የእርስ በዕርስ ጦርነቱ ምክንያት የነበሩት የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻርና ሌሎች የአገሪቱ ፖለቲከኞች አገሪቱን ወደ ተሻለ መንገድ የሚወስዳት ሁኔታ መደራደሩ እንደሆነ መቀበላቸውን የሚያሳይ መሆኑን ጽፏል። በተያዘው 2018 ደቡብ ሱዳን ሰላም የሰፈነባት አገር መሆን የመቻሏ ትልቁ ማሳያ እንደሆነም ነው ጋዜጣው የጻፈው። 

 የፖለቲካ ተንታኙ ፍሬድ ኦሉኦቹ፤ የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች አሁን እየመጡበት የሚገኙት መስመር አገሪቱን ወደ ተሻለ የሰላም መንገድ የሚያመራት መሆኑን ጽፏል። የአገሪቱ የፖለቲካ መሪዎች እንደ አብዛኛው የአገሪቱ ዜጎች ሁሉ የአገሪቱ ሰላም አልባነት ከፍተኛ ጫና ውስጥ እንደከተታቸው ነው ያመላከተው።

ፍሬድ ኦሉኦቹ እንደሚለው ፖለቲከኞቹ ሳይቀሩ ለአራት ዓመታት ያህል ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት መላክ አልቻሉም። የጤና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ከአገልግሎት ውጪ በመሆናቸው የህክምና አገልግሎት ለማግኘት የማይታሰብ ሆኗል። በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል የሚገኘው አርሶ አደር ምንም ዓይነት ምርት እያመረተ አይደለም። ከ2 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለረሃብ ተጋልጧል። የእነዚህ እና ሌሎች ችግሮች መደማመር በአገሪቱን የሚገኙት ፖለቲከኞች ቀድሞ ይዘውት የነበረውን መንገድ እንዲቀይሩ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡

ደቡብ ሱዳንን መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ ያለው ተግባር ውሃ እንዲያነሳ  ስድስት ሚሊዮን ሰዎችን ለማገዝ ከዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች የ172 ቢሊዮን ዶላር ዕርዳታ እንደሚያስፈልግ ዘ ኢስት አፍሪካ ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡ በትምህርት ቤቶች መውደምና መጎዳት፣ በመምህራን እጥረት የተነሳ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን አስታውሷል፡፡

በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን ፤ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አገሪቱ በጦርነት ያጣችውን ማንነቷን መልሳ እንድታገኝ የማቋቋም ተግባራቸውን ሊቸሩ እንደሚገባ መናገራቸውን መረጃው አስፍሯል። በፈረንጆቹ 2018 በሀገሪቱ ትርጉም ያለው ሰላም እንዲሰፍን እየተደረገ ባለው የፀረ-ሽብር ትግል ጋር ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በጋራ ለመተባበር ዝግጁ መሆን እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል። የአገረቱ ቀጣዩ ምዕራፍ በጦርነት የጠፋውን ማንነቷን ወደ መመለሱ እንደሚያዘ ግምም መረጃው ያትታል።

 በናይሮቢ የሚኖረው የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ተንታኙ ጄርቫሲኦ ኦኮት፤ከውስጥ ጮክ ብሎ እየተሰማ የሚገኘው የህዝቡ ጩኸት እንዲሁም ፤ከውጭ ደግሞ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ግፊት የአገሪቱ አብዛኛዎቹ ፖለቲከኞች ዛሬ ላይ እጅ እንዲሰጡ ሳያደርጋቸው አልቀረም ሲል ወቅታዊውን የውይይት ሁኔታ ይናገራል፡፡

 «አንዳንዶቹ የጦርነቱ ማብቃትን እንደ ስጋት በመቁጠር የዕርስ በዕርስ ጦርነቱ ተጋግሎ እንዲቀጥል ፍላጎት አላቸው» ሲል የገለጸው የፖለቲካ ጉዳይ ተንታኙ የአገሪቱ ፖለቲከኞች ወደ መልካም መስመር መምጣታቸው ቢታይም የተንሸዋረሩ ሁኔታዎች መታየታቸውን  ተናግሯል።

 የአገሪቱ ፖለቲከኞች ሙሉ ለሙሉ የአገሪቱን ሰላም አለመፈለጋቸው ተከትሎ  በውይይቱ የተደረሰውን የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ስለመሆኑ ጥርጣሬ ያደረባቸው የፖለቲካ ተንታኞችም መኖራቸው እየተነገረ ነው። ለዚህ ጥርጣሬ እንደ አብነት የሚጠቀሰው ስምምነቱ በተግባር ላይ የሚውለው እስከ መቼ ነው? ለሚለው ጥያቄ መልሱ በውል አለመታወቁ ነው፡፡ የደቡብ ሱዳን ተቃዋሚዎች ስምምነቱ በተፈረመ በቀናት ልዩነት የመንግሥት ወታደሮች ጥቃት ፈጽመውብናል ብለው መክሰሳቸው ተዘግቧል፡፡

ይህም የስምምነቱን እርባና ቢስነት ማሳያ ተደርጎ እየተወሰደ እንደሆነ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚወጡ ዘገባዎች ያሳያሉ።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አዳዲስ ተቃዋሚ ቡድኖች መቀመጫ ያደረጓት ሴንትራል ኢኳቶርያ ግዛት ውስጥ የምትገኘው ላሱ በተቃዋሚዎች ቁጥጥር ሥር የነበረች ቢሆንም፣ መንግሥት አካባቢውን ከተኩስ አቁም ስምምነቱ በኋላ መቆጣጠሩ ተነግሯል፡፡ ይህ ደግሞ በእነ ዶክተር ሪክ ማቻር የሚደገፍ አይደለም፡፡ መንግሥት እርምጃ የመውሰዱ መሳያ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ በዶክተር ማቻር የሚመራው ተቃዋሚ ኃይል ቃል አቀባይ ላም ፖል ጋብርኤል መንግሥትን ለዚህ ተጠያቂ ቢያደርጉም፣ የደቡብ ሱዳን ጦር ቃል አቀባይ ሳንቶ ዶሚክ ቾል በበኩላቸው ጥቃቱን የጀመረው ተቃዋሚው ኃይል እንደሆነና መንግሥት ጣልቃ የገባው የንፁሐን ዜጎችን ሕይወት ለመታደግ እንደሆነ መግለጻቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡

የቅርቡን የተኩስ አቁም ውዝግብን ተከትሎ በመንግሥትና ተቃዋሚ ኃይሎች መካከል የተነሳው አለመግባባት የስምምነት ሂደቱን እንዳይረብሸው ተሰግቷል፡፡ የተቃዋሚ ኃይሎች ቦታዋን መልሰው ለመቆጣጠር መዛታቸው፣ ስምምነቱ በሚፈለገው ደረጃ ተግባራዊ ሳይሆን ሊከሽፍ ይችላል የሚሉም ጥቂት አይደለም፡፡ 

ዳንኤል ዘነበ

Published in ዓለም አቀፍ

በአንድ ወቅት ‹‹መልካም አስተዳደር አሁኑኑ›› የሚል መፈክር በስፋት ይዘወተር ነበር፡፡ ሁሉም ሀረጉን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሲለው ይደመጣል፡፡ መፈክሩን መደጋገሙ ባልከፋ፤ ችግሩ ያለው መፈክሩ የተደጋገመውን ያህል ለተግባራዊነቱ ትንሽ ጥረት ሲደረግ አለመስተዋሉ ላይ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሰብሰቢያ አዳራሽ በርካታ ህዝብ ተገኝቷል፡፡ በከተማዋ በአገልግሎት ዘርፍ ከተሰማሩ በተመረጡ ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ዙርያ የህዝብ አስተያየትን መሰረት ያደረገ የዳሰሳ ጥናት ተካሂዷል፡፡ የዕለቱ አጀንዳ ይህን ውጤት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በማቅረብ ማወያየት ነበር፡፡

የጥናቱ ውጤት በፕሮጀክተር ታግዞ የዕለቱ አቅራቢ ገለጻ ታክሎበት ለተሰብሳቢዎች ቀረበ፡፡ ድክመቶች ጎልተው በታዩበት የጥናት ውጤት ላይ አስተያየት እንዲሰጥ መድረኩ ክፍት ሆነ፡፡ እጃቸውን በማውጣት አስተያየት እንዲሰጡ ዕድሉን ያገኙት ተሰብሳቢዎች ሁሉም ማለት ይቻላል በጥናቱ ከተገኙት ውጪ በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖራቸውን ተናገሩ፡፡

የሚመለከታቸው አካላትም ከመድረኩ ሆነው ለተነሱት ቅሬታዎችና ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጡ፡፡ ችግሮቹ መኖራቸውን አምነው ለመቀበል አልተቸገሩም፡፡ በጥናቱም በአስተያየት ሰጭዎቹም የተነሱት ቅሬታዎች መኖራቸውን አረጋገጡ፡፡ ለችግሮቹ መፍትሔ ለመስጠት ቆርጠው መነሳታ ቸውንና የተለያዩ ስትራቴጂዎችን መንደፋቸውንም ተናገሩ፡፡

ለተወሰኑ ሰዎች አስተያየት የመስጠት ተጨማሪ ዕድል ተሰጠ፡፡ በዕድሜ ገፋ ያሉ አንድ አባት ሌሎቹ የተናገሩት እውነት መሆኑን በመጋራት የበኩላቸውን አስተያየት ሰነዘሩ፡፡ ቃል በቃል ባይሆንም ሃሳባቸው እንዲህ የሚል ነበር ‹‹…የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩ ሁሌም ይጠቀሳል፡፡ ችግሩን ለመፍታት እንደሚሠራም በተደጋጋሚ ይገለጻል፡፡ የሚባለውና የሚነገረው ግን በተግባር አይታይም፡፡ አሁን አሁንማ ይሄ ጉዳይ ሽንገላ እየመሰለ ነው፡፡ የምትናገሩት እውነት ከሆነ የመልካም አስተዳደር እጦትን የመፍታቱ ነገር ከሽንገላ ሊፋታ ይገባል…›› አሉ ጎላና ረገጥ ባለ አገላለጽ፡፡

የመርሀ ግብሩ መሪና ሰብሳቢ ከሁለቱም ወገን የተነሱትን ሃሳቦች በመያዝ ማጠቃለያ ሰጡ፡፡ ችግሮቹን ለመፍታት በሚመለከታቸው አካላት ቁርጠኛ አቋም ሊያዝ እንደሚገባም አስገነዘቡ፡፡ 

በተለያዩ አካባቢዎች በሚደረጉ ህዝባዊ ስብሰባዎች ሁለት ጉዳዮች በተደጋጋሚ ይደመጣሉ፡፡ ከተሰባሳቢውና ከሰብሳቢው ወገን የሚሰነዘሩ፡፡ ተሰብሳቢው በአገልግሎት አሰጣጥ ብልሹነት መማረሩን አጉልቶ ይናገራል፡፡ ‹‹መልካም አስተዳደር የለም›› ይላል፡፡ ሰብሳቢው በበኩሉ ‹‹ የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩን እናውቃለን፤ይህን ለመፍታት እንሠራለን›› ሲል ይሰማል፡፡ ከህዝቡ ጋር እያራራቀን ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግርን መፍታት ትልቁ የቤት ሥራ መሆኑን በአፅንዖት ይገልጻል፡፡

ችግሩ መኖሩን ይቀበላል፤ለመፍትሔ እንደሚሠራም ቃል ይገባል፡፡ ሠዓታት በቀናት፤ ቀናት፣ በወራት፣ ወራት በዓመታት እየተተኩ መንጎዳቸውን ይቀጥላሉ፡፡ የተገባው ቃል ግን ሲተገበር አይታይም፡፡ ትናንት የነበረው የመልካም አስተዳደር እጦት ዛሬም እንደ አዲስ ለውይይት ይቀርባል፡፡ የተገባለት ቃል ተፈፃሚ ያልሆነለት ህዝብ የተሸነገለ ይመስለዋል፡፡ አዛውንቱ እንዳሉት የመልካም አስተዳደር ሽንገላ ይመስላል፡፡ ቅሬታው ይበረታል፤ ኩርፊያው ይጠነክራል፡፡

የመልካም አስተዳደር እጦት ህዝቡን ለከፍተኛ ምሬትና ሮሮ መዳረጉ አደባባይ የወጣ ሀቅ ነው፡፡  ችግሩ በመንደር፣ ወረዳ፣ ክፍለ ከተማ፣ ከተማ አስተዳደር፣ ዞንና ክልል ግዛቱን አስፍቷል፡፡ በምሬት አለንጋ በርካቶችን መግረፉን ተያይዞታል፡፡ የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆነው ህብረተሰብም መፍትሔ ፍለጋ የአቅሙን ያህል ኳትኗል፡፡ ‹‹ባለህበት ሂድ›› ቢሆንበትም፡፡

ሰሞኑን በዝግ ስብሳባ ለመፍትሄ ሲመክር የነበረው የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል፡፡ ህዝቡ ይህን ውሳኔ በጉጉት ነበር ሲጠባበቅ የቆየው፡፡ ‹‹ምን አዲስ ነገር ይዞ ይመጣ ይሆን?›› የሚለው ጉጉትም ቀላል አልነበረም፡፡ በተለይም የዕድገት ነቀርሳ የሆነውን የመልካም አስተዳደር እጦት በመቅረፍ ረገድ፡፡

መልካም አስተዳደር ለህዝቡ ብቻም ሳይሆን ለአገርም የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ በርካቶችን ያስለቀሰውንና እያስለቀሰ የሚገኘውን የመልካም አስተዳደር እጦት ችግር ለመፍታት ጥረቱ በደንብ መጠናከር ይኖርበታል፡፡ ይህ ደግሞ ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው፡፡ ብርቱ ጥረትና ትግል፣ ቁርጠኝነትና ፍላጎት መኖር አለበት፡፡

የጉልበተኛውን አስመራሪ ዳገት ለመናድ የተጀመረው ጥረት በተባበረ ክንድ ሊደገፍ ግድ ይለዋል፡፡ ይህን የብሶት ነበልባል ለማጥፋት ህዝቡ ከመንግሥት ብዙ ጠብቋል፤ይጠብቃልም፡፡ ለዚህም ነው አሁንም የገዥውን ፓርቲ የሥራ አስፈፃሚ ስብሰባ በጉጉት መጠበቁ፡፡

 ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ግምገማ በማድረግና በመፍትሔዎቹ ዙርያ በመወያየት መደምደሚያውን ይፋ አደረገ፡፡ በዚህ ከተካተቱት በርካታ ጉዳዮች አንዱ በህዝቡ በተደጋጋሚ የሚነሳውን የመልካም አስተዳደር ጉዳይ የሚመለከተው ይገኝበታል፡፡

 በአገሪቱ የህልውና ጥያቄ የሆነውን መልካም አስተዳደርን የማስፈን እንቅስቃሴ በአመራር ድክመት የተነሳ ለበርካታ ችግሮች እንደተጋለጠ ሥራ አስፈፃሚ ኮማቴው ማረጋገጡን በመግለጫው አመልክቷል፡፡

በውጤቱም የህዝቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማስፋት፣ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ የግልጽነትና የተጠያቂነት አሠራርን ለማንገሥ፣ ውጤታማና ቀልጣፋ አስተዳዳር ለመገንባት የሚደረገው ጥረት በሚፈለገው ደረጃ እንዳይጓዝ አድርጓል፡፡

 በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት ህዝባዊ አደራቸውን ወደ ጎን በመተው ለግል ጥቅማቸው ሲሯሯጡ ታይቷል፡፡ ይህ በህዝቡ በተደጋጋሚ ሲነሳና እየተነሳ ያለው  ቅሬታ የእውነታ ሚዛኑ ደፍቷል፡፡

‹‹የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት በቅን ልቦናና መንግሥታዊ መመሪያዎችን በተከተለ አኳኋን ህዝቡን የሚያገለግሉና ተሳትፎና ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጡበት ዕድል ቀንሷል፡፡ ከዚህ የተነሳ ከፍተኛ የህዝብ ምሬት ተፈጥሯል፡፡ ሥራ አስፈፃሚው ይህ ችግር ከምንም ነገር በላይ በከፍተኛው አመራር ደረጃ በሚታይ ጉድለት ምክንያት የተፈጠረና የተባበሰ እንደሆነ አረጋግጧል›› የሚለው የሥራ አስፈፃሚው መግለጫ የዚህ አስረጂ ነው፡፡

እናም በአገሪቱ እየተፈጠሩ ላሉት ችግሮች ዋና መንስዔ የሆነውን መልካም አስተዳዳርን የማስፈኑ ጉዳይ አሁኑኑ የመፍትሄ ሃዲዱን ተቆናጦ ጉዞውን ሊያፋጥን ይገባል፡፡ ‹‹ መልካም አስተዳደር አሁኑኑ›› የምትለዋ የቆየች መፈክር በተግባር ልትፈተሽ ይገባል፡፡ በብሶትና ምሬት የተሞላውን የመልካም አስተዳደር እጦት ፊኛን ማስተንፈስ ግድ ይላል፡፡ በምሬትና ቅሬታ አየር የተሞለውን የመልካም አስተዳደር ፊኛ በህዝብ እርካታ ለመቀየር ርብርቡ በደንብ ጠንከር ማለት አለበት፡፡

ህዝቡ በፈቃዱ ድምፁን በመስጠት የሥልጣን ባለቤት ካደረጋቸው አመራሮች ብዙ ይጠብቃል፡፡ ይሠሩልኛል፣ ያገለግሉኛል ባላቸው አካላት መጠቀም እንጂ መጎዳትን አይሻም፡፡ እናም አመራሩ ድክመቶች እንዳሉበት ከተገነዘበ የዚህ እውነታ ማረጋገጫው ድክመቶቹን በተሻሻሉና የህዝቡን ጥያቄዎች በሚመልሱ ውጤቶች መተካት ነው፡፡ ያስመረረውን ህዝብ በመካስ በእርካታ ማንገሥ ይገባል፡፡ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ድክመት መኖሩን አምኖ ይቅርታ እስከ መጠየቅ ከደረሰ ውክልናውን የተቀበለው እያንዳንዱ አመራር ለኮሚቴው ውሳኔ ስኬት ብዙ መሥራት ይጠበቅበታል፤ ግዴታውም ነው፡፡ በተለይም መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፡፡

መልካም አስተዳደርን ማስፈን የአንድ ጊዜ ዘመቻ አይደለም፡፡ በዘላቂነት ሊቀጥል የሚገባው ተግባር እንጂ፡፡ የህግ የበላይነትን በማስፈን ዜጎች በህገ መንግሥቱ የተጎናፀፉት መብት ሳይሸራረፍ ሊከበርላቸው ይገባል፡፡

እንደ ግብር ከፋይነታቸው የሚገባቸውን አገልግሎት በአግባቡ ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህን አገልግሎት ለመስጠት ኃላፊነቱን የተረከበው አመራር ደግሞ የቤት ሥራውን በአግባቡ መወጣት አለበት፡፡ መንግሥትና ህዝብን የሚያቃቅሩ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡና ራሳቸውን ሊያስተካክሉ ግድ ነው፡፡ እንደተባለውም ሽንገላ የሚመስለውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በፍጥነትና በጥራት ለመመለስ ሁሉም የበኩሉን ይወጣ፡፡

ዲዲሞስ

Published in አጀንዳ

ለአስራ ሰባት ቀናት በወቅታዊ ችግሮች ፣ መፍትሄዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙርያ በስፋት ሲመክር፣ ሲገመግምና ሲወያይ የነበረው የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የደረሰበትን ውሳኔ ለህዝቡ ይፋ አድርጓል፡፡

ውሳኔዎቹ ላይ ለመድረስ ጠንካራና ግልጽነትን የተከተለ ግምገማ ማካሄዱንም አስታውቋል፡፡ በአገሪቱ ለተከሰቱት ችግሮች መንስኤው የአመራሩ ድክመት መሆኑንም አምኖ ተቀብሏል፡፡ ችግሮቹንም በግልጽ ለይቶም አስቀምጧል፡፡ አሁን ትልቁ የቤት ሥራ በድል ተጠናቋል፡፡ ችግር ተለይቶ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ተቀይሰዋል፡፡ የአስተሳሰብ አንድነት ተፈጥሯል፡፡

አሁን ቀጣዩ የቤት ሥራ የመፍትሔ አቅጣጫዎቹን ወደ መሬት ማውረድ ነው፡፡ ይህ ዕርምጃ ከባድ አለመሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቱም በገዥው ፓርቲ የሚመራው መንግሥት ባለፉት ጊዜያት ጠንካራ ለውጥ አምጭ ዕርምጃዎችን ሲወስድ ተስተውሏል፡፡ የህዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ ያስችላሉ ያላቸውን ተጨባጭ ስልቶች ቀይሶ በተግባር አሳይቷል፡፡

የቅርቡን መመልከት ቢያስፈልግ እንኳን የመንግሥትን መዋቅር በአዲስ መልክ የማደራጀት ሥራ ተሠርቷል፡፡ ከፍተኛው የመንግሥት ካቢኔ ከገዥው ፓርቲ አባላት ውጪ የሆኑ ምሁራን ለከፍተኛ የመንግሥት ስልጣን ታጭተው ኃላፊነቱን ተረክበዋል፡፡ ይህ ዕርምጃ ከለውጥ ፍላጎት የመነጨ ነው፡፡

 በፖለቲካው መድረክ ብዙም ተሳትፎ ያልነበራቸው ‹‹እናንተ ለዚህ ቦታ ብቁ ናችሁና ህዝብና አገርን በዕውቀታችሁና ልምዳችሁ አገልግሉ›› ተብለው ለሥልጣን በቅተዋል፡፡ ይህን ማድረግ የቻለ ፓርቲ በአስተሳሰብ አንድነት የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ይቸገራል ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ እናም የተላለፉት ውሳኔዎች በተጨባጭ እንዲተገበሩ መሥራት ግድ ይላል፡፡ ውሳኔዎቹ የወረቀት ላይ ነብር ሆነው እንዳይቀሩ ትግሉ ግለቱን ጠብቆ መጓዝ አለበት፡፡ ቃሉ መሬት ረግጦ በተግባር እውን መሆን አለበት፡፡

በመንግሥት የተለያዩ የአመራርነት ዕርከን ላይ ሆነው ኃላፊነታቸውን የዘነጉት አሁንም ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ሊጠየቁ ይገባል፡፡ መንግሥትና ህዝብን ለማቃቃር የሚተጉትንም ሃይ ማለትና ዞር ማድረግ ተገቢነቱ አያጠያይቅም፡፡ የቡድንተኝነት ስሜትን በመላበስ ዜጎችን ለማጋጨት የሚጥሩ ህገ ወጦችን ከዕኩይ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ የሚያስችል አስተማሪ ዕርምጃ መውሰድ ውሳኔውን መተግበሩን ማሳያ ነው፡፡ ስለዚህ ተኩረት ተሰጥቶት መሠራት ያለበት ሥራ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ህዝቡ የድርሻውን መወጣት አለበት፡፡

የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅና ከተጠያቂነት ለመሸሽ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በስታዲየሞች፣ በአዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት እንዲነሳ የሚጥሩና የሚንቀሳቀሱ የህዝብና የአገር ነቀርሳዎችን መዋጋትም በኮሚቴው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ መጥፎ አባዜ የሀገር ህልውናን የሚፈታተንና ከባድ አደጋን የሚያስከትል በመሆኑ  አፅንዖትን ይሻል፡፡ ሕዝቡን በማለያየት ግጭት ለማስነሳት የሚያሴሩ ኃይሎችን ማስቆምም ግድ ይላል፡፡ ተመሳሳይ ችግር ዳግም እንዳይከሰት በውሳኔው መሰረት ሥራዎች መሠራት አለባቸው፡፡

ዜጎች በሠላም ወጥተው በነፃነት የሚንቀሳቀሱበትን ምህዳር ለማጥበብ የሚጥሩትን መመከት ተገቢ ነው፡፡ ከምንም ነገር በላይ ደግሞ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ማንም ከህግ በላይ የሚሆንበት አግባብ መፈጠር የለበትም፡፡ ስለሆነም በሕገ መንግሥቱ መከበር አለበት፡፡ ግጭቶች በተፈጠሩባቸው አካባቢዎች የስውር እጃቸውን ያስገቡ አካላትን የመያዙ ዕርምጃ መወሰድ አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ነው ሰላምና መረጋጋት ማስፈን የሚቻለው፡፡

ገዥው ፓርቲ የህዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስና የተበላሹ አካሄዶችን ለማስተካከል ጊዜ ወስዶ የደከመውን ያህል ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ እንዳለበት አለበት፡፡ ‹‹የተበላሸው ይስተካከላል›› ብሎ መናገር ብቻ ሳይሆን ተስተካክሎ መታየት አለበት፡፡ ‹‹ህግን የጣሱ በህጉ መሰረት ይጠየቃሉ›› የሚለው አገላለጽ ‹‹በህግ ተጠያቂ ሆኑ›› ወደሚል ተግባራዊ ዕርምጃ መለወጥ ይኖርበታል፡፡ ይህ ሲሆን ሌሎች ተመሳሳይ ጥፋት እንዳያጠፉ ትምህርት ያገኛሉ፡፡

በሥራ አስፈጻሚው ውሳኔ ‹‹የህዝብ ጥያቄዎች በፍጥነት ምላሽ እንዲያገኙ ይሠራል›› የሚለው በህዝቡ ‹‹ጥያቄዬ ምላሽ አገኘ›› አስተያየት መቀየር ይኖርበታል፡፡ ውሳኔው ከወረቀት ነብርነት የሚወርደው ይህን በተግባር ማሳየት ሲቻል ነው፡፡

ይህን ለማድረግ ደግሞ ጥሩ ተሞክሮ መኖሩ አይካድም፡፡ ፈታኙን የችግር መንስኤ መለየት ለቻለ ፓርቲ ውሳኔዎቹን መተግበር አያቅተውም፡፡ እናም ውሳኔዎቹ በየደረጃቸው መሬት እየወረዱ፣ ይተግበሩ፡፡ ውጤቶቹም ይፈተሹ፣ ይገምገሙ፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

 አዲስ አበባ፡- አዲሱ የግብፅ ‹‹ዓለም ባንክ ያደራድረን›› አማራጭ የድርድር ሃሳብ ዓለም አቀፍ ተቀባይነትና ህጋዊ መሰረት የሌለው መሆኑን ምሁራን አመለከቱ፡፡

በናይል የትብብር መድረክ (ናይል ቢዝን ኢንሸቲቪ) የምስራቅ ናይል የቴክኒክ አህጉራዊ ፅህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት ግብፅ  የቴክኒክ ሂደቱ አያዋጣኝም የሚል ፍራቻ ካላት በሶስትዮሽ ውይይቱ ላይ ሶስተኛ አካል ብናሳትፍ የሚል ሃሳብ አቅርባ ከሁለቱ አገራት ጋር መወያየት ነበረባት፡፡ ይህ ባልሆነበት ደረጃ በራሷ የዓለም ባንክ ያደራድረን ብላ መምረጧና መወሰኗ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት የሌለውና የተለመደ አሰራር አይደለም፡፡

‹‹ትልቁ ጥያቄ ሶስተኛ አካል ያስፈልጋል ወይ?›› የሚለው ነው የሚሉት አቶ ፈቅ ውሳኔውን ሶስቱ አገራት በጋራ ሆነው የሚወስኑት እንጂ ግብፅ በተናጠል የምትወስነው እንዳልሆነ ገልፀዋል፡፡

መንግስት የዓለም ባንክ ያደራድረን የሚለውን የግብፅ ሃሳብ በጥናት ተንትኖና ከተለያዩ አቅጣጫዎች አይቶ መወሰን እንዳለበት አቶ ፈቅ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ የናይል ጉዳይ በቴክኒክ ደረጃ ብቻ እንዲታይ መወሰን እንዳለባትም ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ ትምህርት ቤት የዓለም አቀፍ ህግ መምህር ዶክተር ደረጀ ዘለቀ በበኩላቸው ድርድር በህግ ማዕቀፍ ውስጥ ባለ ግንኙነት የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት ከሚወሰዱ አማራጮች ውስጥ አንዱ ነው ይላሉ፡፡ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ደግሞ የህዳሴን ግድብ አስመልክቶ የህግ ጥሰት ወይም በህጋዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስገድድ አንዳች የጋራ የህግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ ድርድር የሚለው የግብጽ ሃሳብ ‹‹ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ነው›› ሲሉ ነቅፈውታል፡፡

የአደራዳሪ ጥያቄ እንደማያስፈልግ የጠቆሙት ዶክተር ደረጀ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በታችኛው የተፋሰሱ አገራት ላይ የአካባቢ ተጸእኖ እንደማይኖረው ግምገማ የተደረገውና የመረጃ ልውውጥ የተከናወነው ከበጎ ፈቃድና ለዲፕሎማሲ ግንኙነት ሲባል እንጂ አንዳችም የህግ ግዴታ ኖሮ አይደለም ብለዋል፡፡

ሰሞኑን የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ‹‹ዓለም ባንክ ያደራድረን›› የሚል የድርድር ሃሳብ ይዘው ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ይታወቃል፡፡

 

ጌትነት ምህረቴ

 

Published in የሀገር ውስጥ

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአ ንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ወጪ አራት ዕቃ ጫኝ  ዘመናዊ አውሮፕላኖችን ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ውል ገብቶ እያሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የአየር መንገዱ የካርጎ ከፍል ዋና ሃላፊ  አቶ ፍጹም አባዲ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ  በብድር በተገኘ አንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ወጪ  እያንዳንዳቸው በአንድ ጊዜ 103 ቶን ዕቃ የመጫን አቅም ያላቸው አራት  አውሮፕላኖችን ለመግዛት ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ውል ፈጽሟል፡፡

አራቱ ቦይግ 777 ዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች ከአፍሪካ፣ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ ባንኮችና አበዳሪ ድርጅቶች በተገኘ ብድር የሚገዙ  መሆናቸውን  ጠቅሰው፤ የአውሮፕላኖቹ  ግንባታ ተጠናቆ ቅብ ደረጃ በመድረሳቸው ከመ ጪው ዓመት መስከረም 2011 ዓ.ም ጀምሮ ወደ አገር ውስጥ ይገባሉ ብለዋል፡፡

የደንበኞችን ፋላጎትና የካርጎ አገልግሎቱን ለማጣጣም አየር መንገዱ እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተው፤ አዳዲሶቹ  አውሮፕላኖችም የአገሪቱን የወጪና የገቢ ንግድን ለማቀላጠፍ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል፡፡

አዲሶቹ አውሮፕላኖች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ የአየር መንገዱን የዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች ቁጥር ወደ 12 እንደሚያሳድገው ጠቁመው፤ አየር መንገዱ ከሚያጓጉዛቸው ዕቃዎች መካከል በዋነኝነት የአበባ ምርትን ጨምሮ የግብርና ምርቶች፣ ጨርቃጨርቅና የተለያዩ  የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶችና የመኪና መለዋወጫዎች እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል አየር መንገዱ በአሁኑ ጊዜ በዓመት 350 ሺ ቶን  ዕቃ  የሚያስተናግዱ መጋዝኖች እንዳሉት ገልጸው  በ150 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በዓመት 600 ሺ ቶን ዕቃዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው መጋዘን አስገንብቶ ማጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡ ይህም  የካርጎ አገልግሎቱን የተሻለ እንደሚያደርገው ነው የገለጹት፡፡

በአሁኑ ጊዜ አየር መንገዱ ከ100 ቶን በላይ አቅም ያላቸው ዘመናዊ ስድስት ቦይግ 777 የሚባሉ አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን፤ በጥቅሉ የስምንት ዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች ባለቤት ነው፡፡ በእነዚህም አውሮፕላኖች ወደ 44 መዳረሻዎች በመብረር በዓመት 400ሺ ቶን ዕቃዎችን ያጓጉዛል፡፡

ጌትነት ምህረቴ

 

Published in የሀገር ውስጥ

አዲስ አበባ፤- በዓመት ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ ታካሚዎች የህክምና አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን የማስፋፊያ ስራዎች እየሰራ መሆኑን የቅዱስ ጳውሎስ ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ  አስታወቀ።

የሆስፒታሉ  የግንባታ፣ ቁጥጥር እና የኮንትራት አስተዳደር መሀንዲስ ሞቲ አሰፋ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በሆስፒታሉ  ለእናቶችና ህፃናት ፣ ለካንሰር፣  ለአንጀት እና ለጨጓራ ህክምናዎች እንዲሁም ለአስከሬን ምርመራና ፓታሎጂ ማዕከል ከሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ አምስት ህንፃዎች እያስገነባ ነው።  አዲሶቹ ህንጻዎች አንድ ሺ 220 አልጋዎች ይኖሯቸዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ሆስፒታሉ በዓመት ለ500ሺ ታካሚዎች አገልግሎት እንደሚሰጥ መሀንዲስ ሞቲ ጠቁመው የአዲሶቹ ህንጻ  ግንባታ ሲጠናቀቅ  በዓመት በድምሩ ለአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሰዎች አገልግሎት ይሰጣሉ ብለዋል። 

እንደ መሀዲሱ ገለጻ የእናቶችና ህፃናት ህክምና ክፍል ህንፃ ግንባታ 80 በመቶ ተጠናቋል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የህክምና መሳሪያዎችን በማሟላት ከአራት ወራት በኋላ ስራ ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ግንባታው 99 በመቶ የተጠናቀቀው የአስከሬን ምርምራ ማዕከል መሳሪያዎችን በማስገባት በአንድ ወር ውስጥ ስራ ይጀምራል። የካንስር፣  የልብ፣ የአንጀት እና የጨጓራ ህክምና ማዕከላት ህንጻ ግንባታ 27 በመቶ ደርሷል።

 የህንጻዎቹ ግንባታ ቢፋጠንም  ከዋጋ ግሽበቱ ጋር ተያይዞ እንደ ብረት ያሉ የግብዓት አቅርቦቶች እጥረት መኖሩን መሀዲስ ሞቲ ጠቅሰው ይህም የግንባታ ሂደቱን አስቸጋሪ አድርጎታል ሲሉ አብራርተዋል። 

የካንሰር ህክምና ማዕከሉ አምስት የጨረር ህክምና ታንከሮችና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን  የጠበቁ የህክምና መሳሪያዎች ስለሚኖሩት የዘርፉን ህክምና አንድ ደረጃ ከፍ እንደሚያደርገው መሀንዲስ ሞቲ ተናግረዋል።

የአስከሬን ምርመራና የፓታሎጂ ማዕከል ህንፃ ባለሶስት ፎቅ ሲሆን ሌሎቹ አራት ህንጻዎች ሁለት ምድር ቤትና ባለ ስምንት ፎቅ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ህንፃዎቹ  በ13ሺ ካሬ ሜትር ላይ ያረፉ መሆናቸው ታውቋል። የሆስፒታሉ አጠቃላይ የአልጋዎች ቁጥር ከነባሩ ጋር ሲደመር አንድ ሺ640 ይደርሳሉ፡፡

አጎናፍር ገዛኸኝ

 

Published in የሀገር ውስጥ

 የኢንዱስትሪያላይዜሽን ሽግግሩን ለማፋጠን በ17 ቢሊዮን ብር በአራት ክልሎች የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ ነው፡፡ ለዚህ ከሚያስፈልገው ገንዘብም የፌዴራል መንግሥት ከዘላቂ የልማት ግቦች 5 ቢሊዮን 748 ሚሊዮን 500ሺህ ብር መደቡን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል። ቀሪው 12 ቢሊዮን ብር ደግሞ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በብድር ይሸፈናል።

በሚኒስቴሩ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ተስፋዬ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ለኦሮሚያ ቡልቡላ ሁለት ቢሊዮን 412 ሚሊዮን 200 ሺህ ብር፣ ለአማራ ቡሬ አንድ ቢሊዮን 512 ሚሊዮን ብር፣ ለደቡብ ይርጋለም አንድ ቢሊዮን 407 ሚሊዮን 700 ሺህ ብር፣  ለትግራይ ባዕኸር 412 ሚሊዮን 100ሺህ ብር ተመድቦ የፓርኮቹ ሥራ ተጀምሯል።

በሚኒስቴሩ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ትራንስፎርሜሽን ዳይሬክተር አቶ ሁነኛው አበባው፤ የ12 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር የግንባታ ወጪ የብድር ጥያቄ ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ መቅረቡን ሲገልጹ የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንትና የሊዝ ፋይናንስ ኃላፊ አቶ ተሾመ አለማየሁ ባንኩ የብድር ጥያቄውን እየመረመረ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

ባንኩ የፓርኮቹን ሼዶችና መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት ግንባታ ለሚካሂድባቸው ክልሎች  የ20/80፣ እና በፓርኩ ውስጥ ለሚገቡ  ባለሀብቶች በገንዘብ  ወይም በዓይነት ለማሽኖች ግዥና ለሥራ ማስኬጃ ወጪዎች የ15/85 ልዩ የገንዘብ ብድር ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዕድል ማመቻቸቱንም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

ኦሮሚያ፣ አማራና ትግራይ ክልሎች የግንባታ ቦታ ካሳ ክፍያ ማጠናቀቃቸውን የጠቆሙት አቶ አሰፋ የደቡብ ክልል የካሳ ክፍያ እያከናወነ ነው ብለዋል፡፡ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ግምገማ በማድረግ አርሶ አደሮች ጥራት ያለው ምርት እንዲያመርቱ ስልጠና መሰጠቱንም ገልጸዋል፡፡

የምርት ማሰባሰቢያ ማዕከላት ተለይተው ለግንባታ ዝግጁ ሆነዋል። የኢትዮጵያ ግብዓት አቅራቢ ልማት ድርጅት ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶችን ለመረከብ መመሪያ (ማኑዋል) አዘጋጅቷል። የኢንዱስትሪ ፓርኮቹን ድንበር ለማስከበር ዙሪያቸውን የማጠር ሥራ ከመከናወኑም በላይ ዲዛይናቸውም ተጠናቋል፡፡ ግንባታቸውን ለማከናወን ከሥራ ተቋራጮች ጋር ውል ተገብቷል፤ መሰረተ ልማቶችን ከሚዘረጉ አካላት ጋርም ከስምምነት ተደርሷል ብለዋል፡፡

ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ የሰው ኃይል አቅምን ለማጎልበት ለአራቱም ክልሎች የአሰልጣኞች ስልጠና፤በክልሎቹ ለሚገኙ ሃያ አንድ ዩኒቨርሲቲዎች የንግድ ልማት ስልጠና ተሰጥቷል። የአዋጭነት ጥናት በማድረግ፣ መስፈርቶችን በማዘጋጀት ባለሀብቶችን በመመልመል ለማስገባት ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው። ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ተቋቁመው የሰው ኃይል የማሟላት ሥራ እየተከናወነ ነው።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ ግብርናና እንሰሳት ኮሌጅ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር  ኤርሚያስ መላኩ፤ ተወደደም ተጠላም የአገሪቱ ኢኮኖሚ መሻሻል ካለበት 85 በመቶ ህዝብ የሚሳተፍበት ግብርና ለኢንዱስትሪ ግብዓት በማቅረብ ኢኮኖሚውን ወደ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ማሸጋገር ያስፈለጋል ባይ ናቸው።

የግብርና ማቀነባበሪዎች መከፈት አንዱ ሌላውን በመመገብ የኢንዱስትሪ ሽግግሩ እንዲፋጠን ያደርጋሉ፡፡ የሥራ ዕድልን ከመፍጠር ባሻገር ምርቶች ላይ ዕሴት በመጨመር የውጭ ምንዛሪን ለማሳደግና የተሻለ ገቢ ለማግኘት ያስችላሉ፡፡ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካትና ለዚህ የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት ሚናቸው የጎላ ነው፡፡

ለአርሶ አደሩ፣ ለነጋዴዎች፣ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሀብቶች፣ ለህዝብና ለአገር ትልቅ ፋይዳ አላቸው። ግብርናውን ለማዘመን፣ አርሶ አደሩ ምርትን በጥራትና በብዛት እንደያመርት መነቃቀትን ይፈጥራሉ የሚልም እምነት አላቸው።

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመካኒካልና የኢንዱስትሪ ምህንድስና ፋኩሊቲ ዲን አቶ ሙሉቀን ዘገየም፤ የረዳት ፕሮፌሰሩን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ ማቀነባባሪያዎቹ የኢንዱስትሪያላይዜሽን ሽግግሩን በማፋጠን ለአርሶ አደሩ አስተማማኝ ገበያ ይፈጥሩለታል። የአርሶ አደሩ ትርፋማነትና ተጠቃሚነት ስለሚጨምርም ምርታማነት ያድጋል፡፡

እንደሳቸው ገለጻ የተበጣጠሰው የግብርና ዘዴ ወጥና የተቀናጀ የማምረት አካሄድን ሊከተል ይገባል፡፡ ፋብሪካዎች የሚፈልጉትን ምርት በእቅድ ማምረት፣ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ እርስ በርስ የመመጋገብ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ስኬት ደግሞ የግብርና ቢሮዎች፣ የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት እና የእንሰሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ሚኒስቴሮች፤ እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

በዘርፉ የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ ዋና ዋና ጉዳዮችንም እንዲህ አስቀምጠዋል ‹‹ዘመናዊ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጠት፤ ወጣቶችን በጥቃቅንና አነስተኛ በማደራጀት ለትላልቆቹ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት እንዲያቀርቡ ማድረግ፤ እውቅት ያላቸውን ገንዘብ ካለቸው ጋር በማጣመር ወደ ዘርፉ  እንዲገቡ መሥራት፤ ከኢንዱስትሪ ዘርፍ ትርፍ በረጅም ጊዜ የሚገኙ በመሆኑ ዘርፉን የሚቀላቀሉ ባለሀብቶችን መደገፍ፤ የዘርፉን ባለሙያዎች ማሰልጠን፤ ፋበሪካዎቹ  በእውቅት እንዲመሩ ትኩረት መስጠት፤ ከእርሻ እስከ ፋብሪካ ያለው ሰንሰለት እየተመጋገበ የሚሄድበትን ስርዓት መዘርጋት ፤ ለፋብሪካዎቹ መስፋፋትና ቀጣይነት ጠንካራና የረጅም ጊዜ እቅድ ይዞ መሥራት።››

የጅማ ዩኒቨርሲቲው ረዳት ፕሮፌሰር ኤርሚያስ በበኩላቸው፤ ቀጣይነት ያለው በቂ ግብዓት ማቅረብ፣ቴክኖሎጂን በመጠቀም ምርታማነትን መጨመር፣ ከተለምዷዊ አሠራር ወጥቶ በምርምር መደገፍ፣ ስለዘመናዊ ግብር እና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሰፊ ግንዛቤ መፍጠር ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

በገበያው ተፈላጊ ምርቶችን በጥናት ላይ ተመስርቶ ማምረት፣ ባህላዊና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በድህረ ምርት ጊዜ የሚኖረውን የምርት ብክነት መቀነስ፤ ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያና ማካማቻዎችን በመጠቀም ለፋብሪካዎች ማቅረብ፣ ዩኒቨርሲቲዎች በአስተሳሰብ ቀረጻ፣ በጥናትና ምርምር ከፍተኛ ሚና እንዲጫወቱ መሥራት፤ በምርምር የተገኙ ቴክኖሎጂዎችን በፓርኮቹ መተግበር፤ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ልምድ ካለቸው የውጭ አገር ባለሀብቶች ሽርክና እንዲፈጥሩ ማበረታትም በትኩረት ሊሠራበት የሚገባው ነው ይላሉ - ረዳት ፕሮፌሰር ኤርሚያስ፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው የግብርና ምርቶች ውስጥ 95 በመቶ የሚሆነው እሴት ያልተጨመረበት መሆኑን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ይህን ነባራዊ ሁኔታ ለመቀየር በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የግብርና ምርቶች ባለባቸው አካባቢዎች ለመገንባት ከታቀዱት 17 የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የአራቱ ግንባታ ተጀምሯል።

አገሪቱን ወደ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ለማሸጋገር የግብርና ማቀነባበሪያዎችን መክፈት ወቅታዊም ተገቢም እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ ይህን ማድረግ ካልተቻለ የግብርናው ዘርፍ እያዘገመ የአገሪቱ ዕድገትም በሚፈለገው ፍጥነት ላይጓዝ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው፡፡

ዜና ትንታኔ

አጎናፍር ገዛኸኝ

Published in የሀገር ውስጥ

የአዲስ አበባ ከተማን ጽዳት ለማሻሻል ይመለከተኛል የሚል የኪነጥበብ ባለሙያ ያስፈልጋል ተባለ።   የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጽዳትና ውበት ቢሮ ከኪነጥበብ ባለሙያዎችና ታዋቂ ሰዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።

የውይይቱ ዋና አላማ የከተማዋን ጽዳትና ውበት በዘላቂነት ሊያረጋግጥ የሚችል ተግባር ማከናወን፣ ቆሻሻና ሌሎች ተረፈ ምርቶች ቆሻሻ ሳይሆኑ ጥቅም ላይ የሚውሉ ምርቶች መሆናቸውን ለማስገንዘብ በሚያስችል መልኩ የጥበብ ባለሙያው እንዲሳተፍ ለማድረግ በመፈለጉ ነው የሚሉት የከተማ አስተዳደሩ ሥራ አስኪያጅ ቢሮ ዋና ሥራ እስኪያጅ አቶ ሀይሌ ፍስሃ፤ በከተማዋ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ ያላቸው እንቅስቃሴዎች ይደረጋሉ። ይሁንና በተለያየ አጋጣሚ የኪነጥበብ ባለሙያው ባለው ክህሎት ማህበረሰቡ የእኔነት ስሜት እንዲሰማው ካላደረገ ቀጣይነቱ ስጋት ውስጥ ይገባል። ስለሆነም ማህበረሰቡን ከማስተማር አኳያ ይህ አካል የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።

እንደ ዋና ስራስኪያጁ ገለጻ፤ የመዲናዋ ነዋሪና ከፍጆታ አገልግሎት የሚገኙ ተረፈ ምርቶች በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመራቸው ከተማዋን ፅዱና አረንጓዴ ለማድረግ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ሁሉን አቀፍ ዘመቻ ያስፈልጋል። በተለይ ደግሞ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች በባለሙያዎች የተሰሩ ከሆኑ ውጤታማነታቸው ፍጥነት ያለው እንዲሆን ያግዛል።

የከተማዋን ጽዳት ውብትና አረንጓዴ ልማት በነዋሪውና በመንግስት የተቀናጀ ተሳትፎ በዘላቂነት ለማሻሻል እንዲሁም ለነዋሪዎቿ የተመቻቸ፣ ለጎብኝዎች ሳቢና ተመራጭ ከተማ እንዲሆን የማድረጉ ጉዳይ የአንድ አካል ብቻ እንዳልሆነ የሚያስረዱት ደግሞ ደራሲ ጌታቸው በለጠ ናቸው።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ በንቅናቄው ዓላማና አስፈላጊነት ላይ ማንም ቅሬታ የለውም። ችግሩ አምኖ ተቀብሎ መተግበሩ ላይ ነው። ለዚህ ደግሞ ከመንግስት ጀምሮ ሁሉም የራሱ ድርሻ ቢኖረውም ኪነጥበባዊ ሥራን በመስራት ማህበረሰቡን እያዋዙ ማስተማርና መዝለቁ ወይም ወደ ተግባር የመቀየሩ ሁኔታ ሚዛኑ የሚደፋው የኪነጥበብ ባለሙያው ላይ ነውና የተቻለን አድርጎ መሰረት መጣል ያስፈልጋል።

የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ፤ የአካባቢ ብክለትና የሙቀት መጨመር በሰውና በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ አሁን የአለም አገራት የቆሻሻ መገኛ እያሉ እየሰደቡን ነው። ስለዚህም ከማንወዳደርበት እየተወዳደርን ስለሆነ በጥበብ ማህበረሰቡን እንለውጥ መልዕክታቸው ነው።

የከተማዋን ገጽታ ግንባታ በማሻሻል ለነዋሪዎቿ የምትመችና በአህጉሪቱ ካሉ ከተሞች ተመራጭ ከተማ ለማድረግ ተቋሙ አምስት ሺ የሚደርሱ የጽዳት ባለሙያዎችን የመደበ ሲሆን፤ ከ36 በመቶ በላይ ቆሻሻን ወደ ምርት የመቀየር ስራ መከናወኑ ተነግሯል።

ጽጌረዳ ጫንያለው

Published in የሀገር ውስጥ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።