Items filtered by date: Thursday, 04 January 2018

ከዓለም ህዝብ ውስጥ ከ15 እስከ 24 ዓመት እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ከአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን በላይ እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በአህጉር ሲከፋፈል ደግሞ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 24 የሆኑት  20 በመቶ ያህሉ በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡

በ1996 ዓ.ም በወጣው የወጣቶች ብሔራዊ ፖሊሲ ላይ እንደተመለከተው፤ በኢትዮጵያ ወጣት የሚባለው ከ15 እስከ 29 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲሆኑ፣ በዚህ መሰረት ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 29 ዓመት የሆኑት ከ32 በመቶ በላይ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከ30 ዓመት በታች ያሉ  ዜጎች  ግን ከ70 በመቶ በላይ ናቸው፡፡ በዚህ መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የወጣቶችና የታዳጊዎች ቁጥር መሆኑን ያመለክታል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ‹‹ወጣቶችና የሚሊኒየሙ የልማት ጎሎች›› በሚለው ጥናቱ ‹‹ወጣቶችና የአገራት መንግሥታት›› በሚል ርዕስ ወጣቶችን ስለሚመለከት የተቀመጠው ጽሁፍ እንደሚያሳየው፤ ላለፉት አስርት ዓመታት በርካታ አገራት ወጣቶች ላይ ትኩረት ያደረገ አገራዊ ፖሊሲና ስትራቴጂያዊ እቅድ በማውጣት ተግባር ላይ ለማዋል ተነሳስተዋል፡፡ ሆኖም አብዛኛዎቹ አገራት ወጣቶች ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ አሰራር እንዳልነበራቸውና ውጤታማ በሆነ መልኩ ወጣቶችን የተመለከቱ ዋና ዋና ሥራዎችንም በአግባቡ አልተሠሩም፡፡ በማሳያነት ትምህርት፣ ጤናና የወጣቶች የወንጀል ተጋላጭነት ላይ ትኩረት አልተደረገም፡፡

 ጽሁፉ፣ የህዝብ መጠናቸው ከ50 በመቶ በላይ ወጣት የያዙ አገራት መንግሥታት በጣም በአነስተኛ መጠን የወጣቶችን ኑሮ በሚያከብዱ እንደ ድህነት ቅነሳ ስትራቴጂ ጉዳዮች ላይ የማወያየት ሁኔታ መኖሩንም ይጠቁማል፡፡ ነገር ግን አብዛኛው አገር የረዥም ጊዜ እቅድ በመያዝ በስምምነት ላይ የተመሰረተና ሁሉን ያቀፍ የወጣቶች ፖሊሲ ማውጣት ቢጠበቅባቸውም ወጣቶችን የመዘንጋትና ያልተደራጀ መሆኑን  ያሳያል፡፡

በአፍሪካ ያሉትን ወጣቶች በተገቢው መንገድ መያዝ ካልተቻለባቸው ምክንያቶች መካከል ዋነኛው ድህነት ነው፡፡ በድህነት ቅነሳ መርሃ ግብሮች ሙስናን በመዋጋትና አገራዊ አንድነትን በማስጠበቅ ሥራዎች ላይ የወጣቶች ተሳትፎ አነስተኛ መሆንና ከፍተኛ የሥራ አጥነት ተደማምረው የወጣቶች ሰብዕና ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ወጣቱ በአገሩ ጉዳይ ንቁ ተሳትፎ እንዳያደርግ ማነቆ ሆኖ እስከ ዛሬ ዘልቋል፡፡ የአፍሪካ አገራት ሥራቸውን ከወጣቶች ጋር አለማያያዛቸው የወጣቶቹ ሰብዕና በአግባቡ እንዳይገነባ ምክንያት ሆኗል፡፡ የወጣቶች ሰብዕና ላይ በትኩረት ባለመሠራቱ ለተለያዩ ሱሶች ተጋላጭ አድርጓቸዋል፡፡

ጎጂ መጤ ባህሎችንና አደንዛዥ እፆችን በመከላከል የወጣቶችን ሰብዕና ለመገንባት የተዘጋጀውን የአምስት ዓመት ስትራቴጂ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር በቅርቡ በአዳማ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ይፋ አድርጓል፡፡ በምክክር መድረኩ የሃይማኖት አባቶች፣ የትምህርት ተቋማት ተወካዮች እንዲሁም በርካታ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል፡፡

ስትራቴጂክ እቅዱ፤ በወጣቶች ሰብዕና ላይ የተጋረጡ ችግሮች በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመሩ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ወጣቶች ለችግር ተጋላጭ የሚሆኑበትና ወደ ሱስ የሚገቡበት ፍጥነት እና የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው  ተቋማትም የሚሠሩት ሥራ ጋር እኩል መሄድ አለመቻሉንም ያሳያል፡፡

በእቅዱ እንደተመለከተው፤ የወጣቶችን ሰብዕና ለመገንባት በዋናነት የቤተሰብ ሚና የማይተካ እንደሆነ በማሳየት እስካሁን የወጣቶች ሰብዕና  ለመቅረጽ የተሠሩ ሥራዎች ከቤተሰብ ጋር አልተያያዙም፡፡ ይህ ደግሞ በወጣቶች ሰብዕና ላይ መሠራት የሚገባውን ያህል እንዳይሠራ ምክንያት ሆኗል፡፡ የችግሩ ምንጭና መነሻ ከቤተሰብ ባለመጀመሩ ሥራውን በእቅድ ብቻ እንዲቀር አድርጓል፡፡ ወጣቶች በግንዛቤ እጥረትና በተለያዩ ምክንያቶች ችላ ተብለዋል፡፡ ይህም የወጣቶችን የችግር ተጋላጭነት እንዲጨምር አድርጓል፡፡

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የወጣቶች ሰብዕና ልማት ዳይሬክተር ወይዘሪት እሌኒ ታደሰ፤ የወጣቶች ሰብዕና ግንባታ ሥራ ለመሥራት የተዘጋጀው እቅድ በወጣቶች ላይ የተጋረጡትን ችግሮች ለመፍታት ግብረ ኃይል በማቋቋም መሥራት ማስፈለጉንም ትገልጻለች፡፡ የተዘጋጀውን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ምን እንደሆነ ለማወቅ ጥናት ለማድረግ መሞከሩን በመጠቃቀስ፤  ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በወጣቶች ጉዳይ ላይ ከሚሠሩ 32 መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተውጣጣ ግብረ ኃይል በማቋቋም ወደ ሥራ ለመግባት የሚረዳ መሆኑንም ጠቁማለች፡፡

እቅዱን በትክክል ተግባራዊ ለማድረግ የሚያጋጥሙ መልካም ሁኔታዎችና እንቅፋት የሆኑትን መለየታቸውንም የጠቆመችው ወይዘሪት እሌኒ፤ እቅዱ እንዲሳካ መልካም አጋጣሚ ናቸው ከተባሉት መካከል በየተቋሙ በተናጥልም ቢሆን በጉዳዩ ላይ የተጀመሩ መነሻ የሚሆኑ ሥራዎች መኖር፣ የተቋቋመው ግብረ ኃይል ከተለያየ ዘርፍ መሰባሰቡ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ከየዘርፉ እይታ አንጻር ለመመልከት ማስቻሉ፣ የግብረ ኃይሉ አባላት የጉዳዩ አሳሳቢነት ካለፉት ጊዜያት በበለጠ እየተረዱ መምጣታቸው፣ የግብረ ኃይሉ አባላት በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው መሆኑን ታመለክታለች፡፡

የእቅዱ እንቅፋት ይሆናሉ ተብለው የተለዩት ደግሞ እስካሁን ድረስ ለጉዳዩ አስፈላጊውን ትኩረት እየተሰጠ አለመሆኑ፣ ያሉትን የህግ ማዕቀፎች በአግባቡ አለመተግበርና የህግ ማዕቀፉ ክፍተት እንዲስተካከልና አዳዲስ ህጎችም እንዲካተቱ ከመሥራት አኳያ ክፍተት መኖሩ፣ በጉዳዩ ላይ ግብዓት የሚሆን የተደራጀ የጥናትና ምርምር ሥራ ያለመኖሩ፣ በወጣቶች ዙሪያ በተናጠል የሚሠሩ ሥራዎች መኖራቸው መልካም ቢሆንም በቅንጅት አለመሠራቱ እንዲሁም በትኩረት እንዳይሠራ ምክንያት መሆኑ በጉዳዩ ላይ ቀጣይነት ያለው ሥራ ላይ ከማተኮር ይልቅ ሁሉንም  ችግር ለመፍታት ጊዜያዊ ሥራ ላይ የማተኮር አሰራር መኖሩ ናቸው፡፡

በወጣቶች ላይ የተጋረጡትን ችግሮች የመቀነስና የወጣቶችን ሰብዕና ለመገንባት የሚሠራው ሥራ ውጤታማ እንዳይሆን የሚያደርጉ ስጋቶች ናቸው ተብለው የተለዩት ደግሞ  የአደንዛዥ እፅ መደብሮች በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፉ መምጣታቸውና እየተስፋፉ የሚገኙት ደግሞ በብዛት በመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አቅራቢያ መሆናቸው አንዱ ነው፤ እንዲሁም ወጣቶችን ወደ ሱስ የሚያስገቡ እፆች ከአገሪቱ ኢኮኖሚ ጋር በከፍተኛ ሁኔታ መቆራኘታቸው፣ የአደንዛዥ እፆች ንግድ ከማህበረሰቡ አኗኗርና ገቢ ምንጭ ጋር የተያያዘ መሆኑ፣ ህብረተሰቡ የወጣቶች ሱሰኝነት የሚያስከትለውን ማህበራዊ ቀውስ በአግባቡ አለመረዳት በተጨማሪም የወጣቶች ሥራ አጥ መሆን ለሱስ እንዲጋለጡ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማበርከቱ ተጠቅሷል፡፡

አደንዛዥ እፆችና የወጣቶችን ሰብዕና በተበላሸ መልኩ የሚቀርጹ ሁኔታዎች ተፅዕኗቸውን ማህበረሰቡ በትክክል እንዲገነዘብ መደረግ እንደሚገባና ህብረተሰቡን ለማሳመን ከፍተኛ ሥራን እንደሚጠይቅ ተመልክቷል፡፡ ማህበረሰቡም የእያ፤ዳንዱ ወጣት ሰብዕና መበረዝና ሱስ ውስጥ መዘፈቅ ለአገር የሚያመጣው መዘዝ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ በትክክል ማስገንዘብ ይገባል፡፡

ህብረተሰቡ ሱስ ህመም መሆኑንና በህክምና እንደሚድን ግንዛቤው በጣም አነስተኛ መሆኑን የምትናገረው እሌኒ፤  ወጣቶች ሱስ ውስጥ ከተዘፈቁ በኋላ ማከም እንደሚቻል ህብረተሰቡን የማስገንዘብና ለሱስ እንዳይጋለጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት ቀዳሚ ሥራቸው መሆኑን ትናገራለች፡፡ ወጣቶች በብዛት የሚገኙበትና ለሱስ ተጋላጭ የሚያደርጉ ሁኔታዎችን ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚመከርም ትገልጻለች፡፡ ለመሥራት የታቀዱት ሥራዎች ከበርካታ ተቋማትና ከአገር ኢኮኖሚ አንጻር ከፍተኛ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸውም ጭምር በመሆናቸው ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ በአግባቡ ማቀድ ላይ አሁንም አሳሳቢ መሆኑን ተናግራለች፡፡

ወጣት የወንድወሰን አለበል የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የአራተኛ ዓመት የህክምና ተማሪ ነው፡፡ የወንድወሰን ስትራቴጂው መቀረጹ ጥሩ ጅምር ቢሆንም አሁንም ያልተተኮረበት ነገር መኖሩን ይናገራል፡፡ ወጣቶችን የተመለከቱ በርካታ የምክክር መድረኮች ላይ በየጊዜው ምክክር ቢደረግም ወጣቱ አሁንም በትክክል ያለበት ሁኔታ ምን እንደሆነ የተዘነጋ መሆኑን ይገልፃል፡፡ የወጣቶች ሱሰኝነትን ለመቀነስ የሚሠራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ወጣቶቹን በሚስብ መልኩ መሆኑ የተተኮረበት እንደማይመስል ይጠቅሳል፡፡ በተለይ ወጣቶች የጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ቴክኖሎጂ በመጠቀም በመሆኑ እቅዱ ውስጥ ይህ ለምን እንዳልተካተተ ይጠይቃል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ወጣቶች በከተማ የሚገኙት በአብዛኛው የሚጠቀሙት ማህበራዊ ድረ ገጽ ነው፡፡ ወጣቶች በእንደዚህ አይነት የምክክር መድረኮች ምን እንደተባለና ወጣቶችን የሚመለከት ምን እቅድ እንዳለ አያውቁም፡፡ ስለዚህ ወጣቶችን የሚመለከቱ ሥራዎች በትክክል ወጣቱ ጋር እንዲደርስ ወጣቱ ምን ላይ እንደሆነና በምን መንገድ ማግኘት እንደሚቻል የተተኮረበት አይመስልም›› ሲል ይናገራል፡፡

እቅዱን በሥራ ውጤታማ ለማድረግ የወጣቱ ትኩረቱ ምን ላይ ነው የሚለውን ማወቅ ካልተቻለ አሁንም ሥራው ግቡን እንዳይመታ ያደርገዋል የሚል ስጋት አለው፡፡ ወጣቱ ስለ ራሱ ችግር እንዲነጋገርና መፍትሄ የሚለውንም ከወጣቱ መቀበል እና ወጣቱን መቅረብም እንደሚያስፈልግ ያመለክታል፡፡ የወጣቶችን ሰብዕና ለመገንባት ቴክኖሎጂን መጠቀም በእቅዱ  ውስጥ እንደ ዋነኛ መንገድም መጠቀም ቢቻል መልካም መሆኑንም ይጠቁማል፡፡

በወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት እንግዳወርቅ አያል  እንደሚናገሩት፤ የወጣቶች ሰብዕና ግንባታ ከቤተሰብ አንስቶ እስከ መንግሥት ድረስ የራሳቸው ድርሻ አላቸው፤ ወጣቶች ከቤተሰብ ጋር ያላቸው ቁርኝትና በአገራቸው ላይ ያላቸው አመለካከት ምን ላይ ይገኛል የሚለውን ማጤን ይገባል፡፡ እያንዳንዱ ወጣት ታሪኩንና ባህሉን በአግባቡ እንዲያውቅ ባለመደረጉና አንድ አይነት መግባባት ባለመኖሩ የወጣቱ ችግር የአገር ቀጣይነት ህልውና ጉዳይ መሆኑ እየተዘነጋ ነው፡፡ የወጣቶች ሰብዕናን የመገንባት ሥራ መጀመር አለበት፡፡ ወጣቱ ባህሉን፣ ወግና ሥርዓቱን በአግባቡ እየተነገረው ሊያድግና ካለፈው ትውልድም የሚያየው መልካም ነገር ሊኖር ይገባል፡፡

የአደንዛዥ እፆች እንደ ችግር መቀመጡ መልካም ቢሆንም፤ ይህንን የመቀየሩ ሥራ ግን ቀላል እንደማይሆን ጠቁሟል፡፡ የማህበረሰቡ የገቢ ምንጭ የሆኑትን የአደንዛዥ እፆች ንግድ ሥራን በሌላ የመተካት ሥራው በጣም ከባድ እንደሚሆንና ጊዜ የሚፈጅ በመሆኑ ሌሎች ሥራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባ ይናገራል፡፡

መምህር እንግዳወርቅ እንደሚናገሩት፤ የኢትዮጵያ ወጣቶች ችግር ሲነገር ሁሌም ችግሮችን አስቀድሞ ‹መጤ ባህል› ላይ ማላከኩ ትክክል አይደለም፡፡ የመጤ ባህሎች ያመጡት ተጽዕኖ በትክክል ሳይጠና የችግሮችን ምንጭ ወደ ‹መጤ ባህሎች› ማመዘኑ ትክክለኛው መፍትሄ ላይ እንዳይሠራ ምክንያት ይሆናል፡፡  መጤ ባህሎች  በወጣቱ ሰብዕና ላይ ያለመጡት ተጽዕኖ በትክክል መጠናት ያስፈልገዋል፡፡ የወጣቶች ሰብዕና ጉድለት ምክንያት በቅድሚያ መጤ ባህሎች ናቸው በማለት ከመፈረጅ ይልቅ አገራቸው የኢትዮጵያ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታው በራሱ ለወጣቶች እንደ ጊዜው እንዲራመዱና በግልጽ እንዲነጋገሩ፣ ሃሳባቸውን እንዲገልጹና የመፍትሄ አካል እንዲሆኑ ምን ያህል ዕድል ሰጥቷቸዋል የሚለውን ማጤን ይገባል፡፡

 የሰብዕና ግንባታ ሥራው ወጣቶች በብዛት ከሚውሉበትና ጊዜያቸውን ከሚያሳልፉበት አካባቢ አኳያ የሚመጥን ሥራ መሥራት፣ የሰብዕና ግንባታ ሥራው ከስሩ መሥራት እንደሚገባ፣ የወጣት ሰብዕና ግንባታ ሥራ ሲታቀድ ሱስ ውስጥ የገቡ ወጣቶችን ከሱስ ለማውጣት ብቻ መሆን እንደሌለበት እና ወጣቶች ወደሱስ ለመግባት ዕድሉ የተመቻቸ በመሆኑ አዳዲስ ሱስ ውስጥ የሚገቡ ወጣቶችንም ለመታደግ እቅድ ሊኖር ይገባል ባይ ነው፡፡ ሁሌም ከችግር በኋላ መፍትሄ ሳይሆን አስቀድሞ የችግሩን መንስኤ በመግታት ወጣቶችን የመታደጉ ሥራ በይበልጥ ቢጠናከር መልካም እንደሆነ ይጠቁማል፡፡

ሰላማዊት ንጉሴ

Published in ማህበራዊ

በቅርቡ በኦሮሚያና በሱማሌ ክልሎች አዋሣኝ አካባቢ በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ጥቂት የማይባሉ ዜጎች ለሞትና ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩትም ግጭቱን ሽሽት ሀብት ንብረት ያፈሩበትን ቀዬ ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል፡፡ እነዚህ ዜጎች ታዲያ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ  አካባቢዎች ባሉ መጠለያዎች ተጠልለው በመንግሥት እንዲሁም በበጎ አድራጊ ድርጅቶችና ግለሰቦችም ጭምር ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛሉ፡፡ በእነዚሁ ተፈናቃዮች አያያዝ፥ ቀጣይ ዕጣ ፈንታቸው፥ በድርቅና  በሌሎች አገራዊ አጀንዳዎች  ዙሪያ ከብሄራዊ አደጋ   ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ከአቶ ምትኩ ካሳ ጋር ቆይታ አድርገናል፤ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

       አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ በበጀት ዓመቱ ከያዘው ዕቅድ አኳያ አሁን ያለበት አፈፃፀም ምን ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ይቻላል?

      አቶ ምትኩ፡- ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ዓላማ አኳያ ከአደጋ በፊት የመከላከል፥ በአደጋ ወቅትና ከአደጋ በኋላ መልሶ የማገገም ድጋፍ ነው ለዜጎች የሚያደርገው፡፡ በዚህ አግባብ በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ሦስት የሥራ ግንባሮች ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በዋናነትም በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች መልሰው የሚያገግሙበት ሁኔታ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ሰፊ ሥራ አከናውኗል፡፡ ባለፈው በልግ አብቃይና አርብቶ አደር አካባቢዎች በተደረገው ግምገማ መሰረት ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ስምንት ነጥብ አምስት ሚሊዮን  ዜጎቻችን  ዕርዳታ መስጠት ተችሏል፡፡

       ሁለተኛው ደግሞ  ባለፈው ክረምት ወቅት በነበረው ከባድ ዝናብ ምክንያት በደረሰው ደራሽ ጎርፍና የወንዞች ሙላት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ 100 ሺ ዜጎች ምግብና የምግብ ነክ ያልሆኑ አቅርቦቶችን የማሟላት ሥራም ተከናውኗል፡፡ እነዚህን ዜጎች መልሰው እንዲያገግሙም ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ካለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ በአገሪቱ የኦሮሚያና ሱማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት ከሁለቱም ክልሎች የተፈናቀሉ ወደ 856 ሺ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ አቅርቦት እያደረግን ነው የምንገኘው፡፡ ስለዚህ በጥቅሉ የኮሚሽኑን አፈፃፀም ስናይ በድርቅ፣ በጎርፍና በግጭት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለዕለት ፍጆታ የሚሆናቸውን አቅርቦት የማቅረብ ሥራ በስፋት በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ለመረዳት እንችላለን፡፡

       አዲስ ዘመን፡- የኮሚሽኑ አቅም አደጋን አስቀድሞ ከመከላከል አኳያ ምን ደረጃ ደርሷል?

    አቶ ምትኩ፡- ብሄራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ስትራቴጂ ላይ በተቀመጠው መሰረት  በመከላከልና አደጋውን በማቅለል ረገድ ዋና ተዋናይ አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶች ናቸው፡፡ ኮሚሽኑ የማስተባበር እና ሀብት  የማፈላለግ ሚና ነው ያለው፡፡ በዚሁ አግባብ መሰረት የሚመለከታቸው ተቋማት ዜጎች በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ አደጋዎች እንዳይጎዱ የሚያደርጉ ሥራዎችን በቅንጅትና ተናበው እንዲያከናውኑ የማስተባበር ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከዚህ አኳያ ባጋጠሙ አደጋዎች የተገኘውን ተሞክሮ በመቀመርና የሚሰጠውን ድጋፍ  ተደራሽነት በማጎልበት ረገድ አቅሙን እያጎለበተ ነው የሚገኘው፡፡

     ከዚህ አኳያ ዋናው ሥራ የአስፈፃሚ ተቋማት ቢሆንም፤ በተለይም የሚሠሩ የልማት ሥራዎች በዋናነትም ድርቅን ከመከላከል አኳያ ዜጎችን ማዕከል ያደረጉ እንዲሆኑ ኮሚሽኑ የበኩሉን ሚና ይወጣል፡፡ ለአብነት ያህል እንኳ ብንጠቅስ ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች የውሃ እቀባ ሥራ አስቀድመው እንዲያከናወኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ይመክራል፤ ይሠራል፤ ያስተባብራልም፡፡ በአርብቶ አደር አካባቢዎችም የመኖ ማምረቻዎች በርከት ብለው እንዲገነቡ  የበኩሉን ጥረት ያደርጋል፡፡

      አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት የድርቅ ተጎጂዎች ቁጥር ምን ያህል ደርሷል? ካለፈው አንፃርስ ሲተያይ እንዴት ይገለጻል?

      አቶ ምትኩ፡- በመላው አገሪቱ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ካለፉት ጊዜያት አንፃር ዘንድሮ  የድርቅ ተረጂዎች ቁጥር ይቀንሳል የሚል ትንበያ አለ፡፡ በተለይም ባለው ክረምት ወቅት ከፍተኛውን የህዝብ ቁጥር የሚይዙት የደጋና ወይና ደጋ አካባቢዎች በቂ ዝናብ በመዝነቡና  ምርቱም በስፋት በመመረቱ የዕርዳታን እጅ የሚጠብቁ ሰዎች መጠን ያንሳል የሚል እምነት አለን፡፡ ስለዚህ  የተረጂዎቹ ቁጥር  ከአምስት እስከ ሰባት ሚሊዮን ብቻ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት ትክክለኛውን ቁጥር በአግባቡ ተደራጅቶ ክልሎችና የፌዴራል መንግሥት ተማምነው ሲያፀድቁት ይፋ የምናደርገው ይሆናል፡፡

       አዲስ ዘመን፡- እነዚህን ተረጂዎች በአገር ውስጥ አቅም ለመደገፍ የሚደረገው ጥረት ምን ይመስላል?

     አቶ ምትኩ፡- እንደሚታወቀው አገራችን ሦስት ተዋናዮች ነው ያሏት፡፡ አንድ መንግሥት ራሱ ሲሆን፣ የዓለም የምግብ ፕሮግራምና ከዚያ ባሻገር ደግሞ ሌሎች የልማት ድርጅቶች በዕርዳታ አቅርቦቱ ተዋናይ ይሆናሉ፡፡ እነዚህ አጋር ድርጅቶች ከዚህ ቀደም ከመንግሥት ጋር የገቡት ስምምነት የሚጠበቅ ነው የሚሆነው፡፡ መንግሥት ሲባል የክልል መንግሥታትና የአገር ውስጥ ባለሀብቱንም ጭምር ሲሆን፣ በአገር ውስጥ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ሀብት መጠቀምም የግድ ይላል፡፡

       አዲስ ዘመን፡-  ከዚህ ቀደም በተለይም በደቡብ ክልል አንዳንድ ቦታዎች በተነሱ ግጭቶች የተፈናቀሉ ዜጎች በምን ሁኔታ ላይ ነው የሚገኙት? 

     አቶ ምትኩ፡- በግጭቱ ወቅት አስቸኳይ ዕርዳታ ከተሰጣቸው በኋላ ግጭት በተነሳባቸው አካባቢዎች የሰላምና ልማት ኮንፍራንስ ተደርጎ ከህዝቡ ጋር መተማመን ላይ በመደረሱ ወደቀያቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ ወደቀድሞው ሰላምም በመመለሳቸው ነዋሪዎቹ መደበኛ ኑሯቸውን እየኖሩ ነው የሚገኙት፡፡

       አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ በኦሮሚያና ሱማሌ ክልሎች መካከል በተነሳው ግጭት ምክንያት ከመኖሪያ አካባቢያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች እየተደረገ ያለው ድጋፍ ምን ያህል ተደራሽ ነው ተብሎ ይታመናል?

     አቶ ምትኩ፡-  አስቀድሜ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በአሁኑ ወቅት እንደ ትልቅ ሥራ ትኩረት ተወስዶ እየተሠራ ያለው ሥራ በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልልና በኦሮሚያ ክልል መካከል አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን መደገፍ ላይ ነው፡፡ በዚህ ግጭት ሳቢያ በኦሮሚያ ክልል  615 ሺ እንዲሁም በሱማሌ ክልል 241 ሺ  በድምሩ 856 ሺ ለሚሆኑ ዜጎች የምግብና ምግብ ነክ ያሉ ግብዓቶችን እንዲያገኙ በማድረግ ላይ ነን፡፡

       በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ እነዚህን ተፈናቃዮች መልሶ የማቋቋም ሥራ ከድጋፉ ጎን ለጎን እየተካሄደ ነው የሚገኘው፡፡ በእቅዱ መሰረት በአሁኑ ወቅት የኦሮሚያ ክልል ተወላጆችን  በክልሉ በሚገኙ 12 ከተሞች የማስፈር ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ በዋናነትም በፊንፊኔ ዙሪያ ባሉ ከተሞች እንዲሁም በሃዋሳና ሻሸመኔ መካከል በሚገኘው ቢሻን ጉራቻ በሚባለው አካባቢ መልሶ የማቋቋሙ ሥራ በስፋት እየተከናወነ ነው፡፡ ይህ ሥራ እንግዲህ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰሞኑን በሰጠው አቅጣጫ መሰረት በሱማሌ ክልልም ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው የሚሆነው፡፡

      አዲስ ዘመን፡- ተፈናቃዮቹን በዘላቂነት ወደቀያቸው ለመመለስ እየተደረገ ስላለው ጥረት ቢያብራሩልን?

     አቶ ምትኩ፡-  ከዚህ አኳያም በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው የሚገኙት፡፡ በዋናነትም በዘላቂነት ከማስፈር ባለፈ ለሥራ ፈጠራ ምቹ የሆነ እቅድ በብሄራዊ አደጋ መከላከልና ዘግጁነት ቴክኒክ ኮሚቴ ተዘጋጅቷል፡፡ እቅዱ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊትም የተፈናቃዮቹን በጎ ፈቃድ የሚያሻ በመሆኑ የሥነ ልቦና የማማከር ሥራ በባለሙያዎች እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም የሰላምና የልማት ኮንፈረንስ የሚካሄድ ሲሆን፣ በዚህም በሚገኘው ግብዓት በተፈናቃዮቹ ፍላጎት  መሰረት በዘላቂነት የማስፈሩ ሥራ የሚሠራ ይሆናል፡፡ 

      አዲስ ዘመን፡- በዚህ ሥራ ላይ የክልሎችን ድጋፍ እንዴት ይገልጹታል? ተናቦና ተቀናጅቶ  ከመሥራት አኳያ ያጋጠመ ችግር የለም?

      አቶ ምትኩ፡-  ይህ ሥራ እንግዲህ የሚሠራው በኮሚሽኑ ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡  ጉዳዩ አገራዊ እንደመሆኑ ግጭቶችን አስቀድሞ ለመከላከልና ከተከሰቱም በኋላ ጉዳታቸው አነስተኛ ይሆን ዘንድ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው ብሄራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቴክኒክ ኮሚቴ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፡፡ በዚህ ኮሚቴ ውስጥ የተለያዩ ባለድርሻ ተቋማትና ክልሎች የሚሳተፉ በመሆናቸው በእቅዱ አፈፃፀም ላይ የበኩላቸውን ሚና እየተጫወቱ ነው፡፡ በተለይም ግጭቱን በአፋጣኝ ከማስቆም አኳያ መከላከያ እንዲሁም የፌዴራልና የክልል የፀጥታ ኃይሎች ጉልህ አስተዋፅኦ ነበራቸው፡፡ ምላሽ የመሰጠቱና መልሶ የማቋቋሙም ሥራ በክልሎች የነቃ ተሳትፎ ነው እየተከናወነ ያለው፡፡

       በሌላ በኩል ደግሞ የአደጋ ዝግጁነት ቢሮ በሁሉም ክልሎች እስከ ቀበሌ ድረስ በተዋረድ የተቋቋመ በመሆኑ እቅዱም ሆነ የሚሰጡት አቅጣጫዎች በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንዲከናወኑ ነው የሚደረገው፡፡ በዚህ ረገድ የታየ ክፍተት የለም፡፡ በተለይም የዕርዳታ አቅርቦቱና ስርጭቱ በክልል መስተዳድሮቹ የሚመራ በመሆኑ ተጎጂዎችን በሚገባ ተደራሽ ማድረግ ተችሏል፡፡

      አዲስ ዘመን፡- እስካሁን ባለው ሂደት በወረርሽኝ መልክ በሽታ እንዳይስፋፋ በእናንተ በኩል እየተደረገ ያለው ጥረት ምን ይመስላል?

      አቶ ምትኩ፡- እንደተባለው በሽታዎች ሊከሰቱ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ስለመሆኑ ከዚህ ቀደምም በድርቅ የተገኘ ተሞክሮ አለ፡፡ በርከት ያሉ ሰዎች በአንድ ካምፕ ሲሰባሰቡ ከአቅርቦትና ከተለያዩ አገልግሎቶች አለመሟላት ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ችግሮች አሉ፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግ  የብሄራዊ ኮሚቴው አባል  የሆነው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር  ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት በመደባቸው የጤና ባለሙያዎች አማካኝነት የክሊኒክ አገልግሎት በየጣቢያዎቹ ለሚገኙ ተረጂዎች እየሰጠ ነው፡፡ ስለዚህ እስከአሁን ድረስ  በወረርሽኝ መልክ የተከሰተ ምንም ዓይነት በሽታ የለም፡፡  ከዚህ በተጨማሪ የስነ ልቦና የማማከር ሥራውም በባለሙያዎች ነው እየተሠራ ያለው፡፡

አዲስ ዘመን፡-  ተፈናቃዮቹን ወደሚፈልጉበት አካባቢ የማስፈሩ ሂደትና በሚሰፍሩበት አካባቢ ደግሞ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እንዳይከሰት የሚደረገው ጥንቃቄ ምን ያህል ነው?

      አቶ ምትኩ፡- አሁን የተፈለገው አዲስ አበባ ዙሪያ መሆኑ ሳይሆን፤ ለማስፈር ምቹ መሆኑ ላይ ነው፡፡ ከአዲስ አባባ በተጨማሪ ባቱ፣ ሻሸመኔና በሌሎችም ከተሞች ላይ የሚሰፍሩ ነው የሚሆኑት፡፡ በቀጣይ ደግሞ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን ሥራው በምክክር የሚሠራ ይሆናል፡፡ ዋናው ግን ሥራ ለመፍጠር ምቹነቱን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ የሰዎችን ዝንባሌ መሰረት አድርገን ነው ሥራ የምንፈጥረው፡፡ በተጨማሪም የመሰረተ ልማት ሥራዎች አብረው የሚሟሉ ይሆናሉ፡፡ በዚሁ አግባብ በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል ወደ ስድስት ኮሚቴዎችን አቋቁመዋል፡፡ መሰረተ ልማት ብቻ ሳይሆን የምግብ አቅርቦት፥ ገቢ አሰባሰብና የመሳሰሉትን ሥራዎች የሚሠሩ ይሆናል፡፡

      አዲስ ዘመን፡-  በቀጣይ ሰላምን አረጋግጦ ተፈናቃዮች ሰላማዊ ህይወታቸውን እንዲቀጥሉ ከማድረግ አኳያ ከማን ምን ይጠበቃል?

      አቶ ምትኩ፡- በዚህ ጉዳይ ዋናው ተዋናይ ህዝብ ነው፡፡ ህብረተሰቡ ደግሞ በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደምንረዳው ሰላም ፈላጊ ህዝብ ነው፡፡ በመቻቻል የሚያምን፣ ተቻችሎ የኖረ አሁንም እየኖረ ያለ ህዝብ ነው፡፡ ትልቁ እሴታችን ይሄ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ከህዝብ ጋር ማሳካት እንደሚቻል ሙሉ እምነት ተይዟል፡፡

       በሌላ በኩል ከህዝብ የተደበቀ ምንም ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ሰላም የሚያውኩ አካላትን ህዝቡ ጠንቅቆ ያውቃቸዋል፡፡ በተጨማሪም በዚህ መንግሥት በኩል ደግሞ ቁርጠኝነቱ አለ፡፡ ስለዚህ ህዝብና መንግሥት በጋራ በመሆን ተግባራዊ የሚያደርጉት ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ ሊታሰብ የሚገባው ጉዳይ ከአገራችን ብዝሃነት አኳያ የአገራችንን ህልውና ለማስቀጠል ለሰላምም፣ ልማትም ለዴሞክራሲም ግዴታ አስፈላጊ ናቸው፡፡ ስለዚህ ለልማትና ዴሞክራሲ መኖር ደግሞ የሰላም መሰረት ነው፡፡ የአገራችንን ልማት ቀጣይነት ለማረጋገጥም ህብረተሰቡ ተረጋግቶ እንዲኖርም ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን የሚሠራ ነው የሚሆነው፡፡

        አዲስ ዘመን፡- እንደስጋት የሚያነሱት በተለይ ተቋሙ ተልዕኮውን ከማስፈፀም አኳያ ተግዳሮት የሆኑበት ጉዳዮች ይኖሩ ይሆን?

      አቶ ምትኩ፡- ከዚህ አንፃር ዋና ተግዳሮት ብለን ያስቀመጥነው የግጭቱ ስፋት ነው፡፡  ከመኢሶ ይነሳና እስከ ሞያሌ ነው የሚደርሰው፡፡ ይህ ማለት ወደባሌ ሲኬድ መዳወላቦ አለ፤ ምሥራቅ ጉጂ አካባቢ እስከ ሞያሌ ይመጣል፡፡ ስለዚህ የቆዳ ስፋቱና ርቀቱ በጣም ፈታኝ ነው የሚሆነው፡፡ ዕርዳታ ሲኬድ በፀጥታ ኃይሉ መጠበቅ ስላለበት መከላከያ እንዲሁም የፌዴራል ፖሊስን ተይዞ ነው የሚኬደው፤ ይህም በራሱ ሥራውን ከባድ ያደርገዋል፡፡

     አዲስ ዘመን፡- በፀጥታ ችግር ምክንያት ዕርዳታውን በማጓጓዝ ሂደት የተስተጓጎለበት አጋጣሚ አለ?

     አቶ ምትኩ፡- አዎ፤ አንዳንድ ቦታዎች ላይ በአንዳንድ ፀረ ሰላም ኃይሎች  መንገድ በመዘጋቱ ምክንያት ዕርዳታው ለተፈናቃዮች በታሰበው ጊዜ እንዳናደርስ እንቅፋት ሆኖብን ነበር፡፡ ይሁንና ከክልሎች ጋር በመነጋገር በሦስትና በአራት ቀናት ውስጥ ችግሩ የሚፈታበት አግባብ ነበር፡፡

      አዲስ ዘመን፡-  ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ !     አቶ ምትኩ፡- እኔም አመሰግናለሁ !

ማህሌት አብዱል

Published in ፖለቲካ

በሲሲና ግብርና ምርምር ማዕከል የጥምር እርሻና ደን ተመራማሪና የስራ ሂደት ተጠሪ ቢቂላ መንግስቱ፤ በምርምር ስራቸው ካካተቷቸው መካከል አንዱ፣ ዝርያው በመጥፋት ላይ ያለውን ጥቁር እንጨት እንዳይጠፋ የማላመድ እና የማስፋፋት ሥራ ነው፡፡

ተመራማሪ ቢቂላ እንደሚናገሩት፤ በባሌ ዞን ደሎ መና ወረዳ ጭሪ በምትባል ቀበሌ ጥቁር እንጨት የሚባለውን የዛፍ ዝርያ የማላመድ ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ ሥራው የተጀመረው እንደ ባሌ ዞን አሊያም እንደ ኦሮሚያ ክልል ብቻ ሳይሆን፤ እንደ አገር ነው፡፡ ምክንያቱም የጥቁር እንጨት ዝርያዎች እንደአገር እየጠፉ ስለሆነ ስጋት ተፈጥሯል፡፡ በመሆኑም ይሕን ስጋት ለማቃለል ብሎም  ተጠቃሚ ለመሆን ዝርያዎቹን ከተለያዩ ከአምስት ቦታዎች ማለትም ከቦንጋ፣፣ ከመናገሻ፣ ከጅባት፣ ከያዩ እና ከጌዶ ለማሰባሰብ ጥረት ተደርጓል፡፡ 

የማላመዱ ሥራ በሦስት የሙከራ ሥራ የተሰራ ሲሆን፣ በማላመድ ሂደት ውስጥ የተለያየ አይነት ደረጃዎች ይወሰዱ ነበር፡፡ በተለይም ክብደቱን፣ ቁመቱን እንዲሁም ከበሽታ ጋር ያለውን ሁኔታ ጨምሮ መረጃ ተሰብስቦ አሁን ለሚታየው ቁመና መብቃቱን ነው ተመራማሪው የሚናገሩት፡፡ ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ይላሉ ተመራማሪው ‹‹ይህ ጥቁር እንጨት የተለያየ ጥቅም ያለው ሲሆን፣ በተለይ በመድሃኒት ፋብሪካ ውስጥ እንደግብዓት ሆኖ የሚያገለግል ንጥረ ነገር በውስጡ የያዘ ነው፡፡ በዚህም የገቢ ምንጭ ሆኖ አርሶ አደሩን ብሎም አገሪቱን እንዲጠቅምና ወደ ስርዓት ለማስገባት ታስቦ እየተሰራ እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡

በዚህ ሥራ ውስጥ በሌላኛው ደረጃ እየተጠና ያለው የጥቁር እንጨቱ ኬሚካል ይዘት ምን ይመስላል? የሚለውም ሲሆን፣ በዚህ ሂደት ውስጥ ቅርፊቱንና ቅጠሉን በመውሰድ ከተለያየ ቦታ የመጣው ዝርያ በተፈጥሮው እዚህ አካባቢ ካለው ዝርያ ጋር ሲተያይ ምን ይመስላል ? የትኛው  ተባዝቶ ወደ ስርዓቱ አሊያም ወደ አርሶ አደሩ ችግኙ ተባዝቶ ቢገባ የተሻለ ነው  የሚሆነው? እንዲሁም አካባቢን ከመጠበቅ አልፎ የገቢ ምንጭ ሆኖ ሊያገለግል የሚችለው ? በሚል  እያጠኑ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡

እንደ ተመራማሪ ቢቂላ አባባል፤ ከተለያየ ቦታ የመጡት አምስቱም ዝርያዎች የተለያየ አይነት ሁኔታ ነው እያሳዩ የሚገኙት፡፡  እድገታቸው መልካም ስለሆነ ብቻ ዝርያው ይስፋፋ ማለት አይቻልም፡፡ ሙሉ ለሙሉ እውቅና እና ይሁንታ ሊያገኝ የሚችለው ከበሽታ የጸዳ መሆኑ፣ የእድገቱ ሁኔታ እንዲሁም ከንጥረ ነገር ይዘቱ ጋር ተያይቶ ተቀባይነት ሲያገኝ  ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም እንደማንኛውም የእህል ዝርያ ጥቅም እንዲኖረው ብሎም አርሶ አደሩ የኢኮኖሚው ተጠቃሚ እንዲሆን ነው በመሰራት ላይ ያለው፡፡ ስለዚህም ምርምሩ በቤተ ሙከራ ላይ ነው ያለው፡፡

ምርምሩ የተጀመረው እንደ አገር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ሥራ ደግሞ ተመራጭ የሆነው የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል ነው፡፡ አንደሚታወቀው እንጨቱ እየጠፋ ያለ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ደሎ መና አካባቢ ያለው የተፈጥሮ የጥቁር እንጨት ዝርያ አለ፡፡ ያንን ለማግኘት ደግሞ በብዙ ኪሎ ሜትር መጓዝን ይጠይቃል፡፡ ከዚህም የተነሳ የምርምር ማዕከሉ በራሱ ናሙና ለመውሰድ በጣም ተቸግሮ እንደነበርም ነው ተመራማሪው የሚናገሩት፡፡ እንጨቱ በባህሪውና በአፈጣጠሩ በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ በአርሶ አደሮቹ ተመራጭ ነው፡፡ ለቤት ምሰሶነት በመመረጡም ካለበት ድረስ በመሄድ ስለሚቆርጡት ለምርምር ሥራው ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት በጣም ፈታኝ አድርጎታል፡፡ ይህም በመሆኑ ነው ወደማላመዱ ሥራ የተገባው፡፡

እንደ አገር ሃሳብ የቀረበው የማላመዱ ሥራ በተለያየ የአየር ጸባይና በሽታንም የመቋቋም ችሎታ እንዲኖረው ታስቦ ነው በደሎ መና በመሰራት ላይ የሚገኘው፡፡ ቦታውም ለዚህ ሥራ በእስካሁኑ ሂደት ውጤታማ መሆኑንም አቶ ቢቂላ ያመለክታሉ፡፡ ይሁንና ይላሉ ተመራማሪው ምንም እንኳ ከቦታው ምቹነት የተነሳ ቢላመድም ስራው አበቃ ተብሎ መቀመጥ የለም፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት፤ እንጨቱ ለአካባቢ ጥበቃ ከሚጫወተው ሚና በተጨማሪ ሌላ ተግባር አለው፡፡ ቅርፊቱ ይፋቅና ከደረቀ በኋላ ወደ ውጭ አገር በመላክ የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል፡ ለአብነት አፍሪካዊቷን አገር ካሜሩንን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ካሜሩን የዚህን ጥቁር እንጨት ቅርፊት በወጪ ንግዷ ውስጥ አካታዋለች፡፡ የአንድ ኪሎ የጥቁር እንጨት ቅርፊትም እስከ መቶ ዶላር ይሸጣል፡፡ እንዲያም ሆኖ በጣም እጥረት መኖሩ ነው የሚነገረው፡፡

ከአንድ ጥቁር አንጨት በየጊዜው ቅርፊቱ እየተገፈፈ የሚነሳለት ከሆነ ቋሚውንስ አይጎዳውም ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄ ተመራማሪው ምላሽ ሲሰጡ እንደተናገሩት፤ አይጎዳውም፤ የራሱ የሳሰድ ደረጃ አለው፡፡ ለምሳሌ ቅርፊቱን ለመውሰድ የእንጨቱ እድሜ ቢያንስ ከተተከለ በኋላ አስር ዓመት ሊሞላው ግድ ይላል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የተፈለገውን ይዘት ይይዛል ተብሎ የሚታሰብበት ጊዜ በመሆኑ ነው፡፡ ቅርፊቱ ሲወሰድም የእንጨቱ ዋና ግንድ ከመሬት አንድ እና ከዛ በላይ ሜትር ከፍ ብሎ ነው፡፡ የሚወሰደውም ከቅርንጫፉ ሳይሆን ከዋናው ግንድ ላይ ሲሆን፣ ቅርፊቱ በተወሰደ በሁለት ወራት ውስጥ ደግሞ ግንዱ ማገገም ይችላል፡፡ ይሁንና ከአንድ ጥቁር እንጨት ላይ ቅርፊቱ በየሁለት ዓመቱ ቢነሳ ነው አማራጭ የሚሆነው፡፡

እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው አገሪቱ ክፍል የሚገኘው አርሶ አደር ከሳር ክዳን ቤት በመውጣትና ወደ ቆርቆሮ ቤት በመሸጋገር ላይ ነውና እንጨቱን እምበዛም ለምሰሶነት ላይጠቀም ይችላል፡፡ ስለዚህ የጥቁር እንጨቱን በማላመድ ማስፋፋት የተፈለገበት ዋና ዓላማ ቅርፊቱን ወደውጭ በመላክ ዶላር እንዲያስገኝ ነው? ተብሎ ለተነሳው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ፤ ምንም እንኳ አርሶ አደሩ ኢኮኖሚው ዳብሮ ከጎጆ ቤት ሥራ ቢወጣም እውነታው ግን ይህ እንጨት አሁንም ተፈላጊ በመሆኑ መጥፋቱ ነው፡፡ ምክንያቱም እናት ዛፍ ከጠፋ ልጁን ማግኘት አይቻልም፡፡ አርሶ አደሩም ቢሆን ለማንኛውም ፍጆታው በአካባቢው ያለውን ነው እንደ ግብዓት የሚጠቀመው፡፡ ስለዚህም የአካባቢን ስነ ምህዳር ለመጠበቅም እንዲሁም ዝርያው እየጠፋ በመሆኑ በዋናነት ለመታደግም ጭምር ነው እየተሰራ ያለው፡፡ ጎን ለጎንም በአካባቢው ያለ አርሶ አደር በኢኮኖሚው ተጠቃሚ መሆን ስለሚችልም ነው፡፡

አቶ ቢቂላ እንደተናገሩት፤ በማላመድ ደረጃ ያለውን ሂደት አጠናቀዋል፡፡ አሁን በዛፉ ላይ ያለውን የኬሚካል ይዘት ደረጃ ሲያውቁና ሙሉ መረጃ በእጃቸው ሲኖር ለአርሶ አደሩ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ቀጥሎ ይሰራል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን በእስካሁኑ ጉዞ በአካባቢው ያለው አርሶ አደር ክትትል ሲያደርግ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ የማላመድ ስራው በሚሰራ ቀበሌ ያሉት ግንዛቤውን በማግኘት ላይ ናቸው፡፡ ነገር ግን በአገር ደረጃ ለማውጣት ሂደቱ ገና ነው፡፡ በእስካሁንም ሙከራ እያደረጉ ያሉት የሌሎች አገሮችን ልምድ ሲሆን፣ ይህንንም እያዩ ያሉት ከወጡት ጽሁፎች በመቀመር እንጂ በቦታው ተገኝተው ምንም አይነት ልምድ አግኝተው አይደለም፡፡ ሥራው በአገር ደረጃ አዲስ ሲሆን፣ ከወንዶ ገነት ምርምር ማዕከል ጋር በጋራ በመሆን ነው የሚሰሩት፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ከባዮሎጂ ክፍለ ትምህርት ጋር የሀሳብ ልውውጥ በማድረግ ላይም ይገኛሉ፡፡

አርሶ አደር አደም ሁሴን በባሌ ዞን፣ ደሎ መና ወረዳ የጭሪ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ከግብርና ስራቸው በተጨማሪ በቀበሌያቸው ውስጥ በመላመድ ላይ ያለውን የጥቁር እንጨት ዛፍ በመጠበቅ ያገለግላሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮች ቀደም ባሉት ጊዜያት ለዛፎቹ የሚደረገውን ጥበቃ በማስተዋል ምን የሚሉት ቅብጠት ነው ለዛፍ ይህን ያህል ጥበቃ የሚደረገው ይሉ ነበር፡፡ አሁን አሁን ግን ግንዛቤውን በማግኘት ላይ ይገኛሉ፡፡ ዶላር የሚያስገኝ በመሆኑ ይጠቅመናል ወደሚለውም ተሸጋግረዋል፡፡ በቀበሌያቸውም የደን ልማት ማህበር በመቋቋሙ ግንዛቤያቸው ጨምሯል፡፡ ዛፍ ደግሞ ህይወት ነው፤ ይሕን አስቀድመው የሚያውቁት ጉዳይ ነውና እየተካሄደ ያለውን የማላመድ ጅማሬ ይደግፉታል፡፡

‹‹ሥራው በአካባቢው የተጀመረው በ1999 ዓ.ም ነው፡፡ አርሶ አደሮችም ይህ አይነቱ ሂደት ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው መሆኑን ከተረዱና ዛፉ ለመድሃኒትነት የሚያገለግል ከሆነ ሥልጠና ተሰጥቷቸው እነርሱም የትሩፋቱ ተቋዳሽ መሆን ይፈልጋሉ›› ሲሉ አርሶ አደር አደም ይናገራሉ፡፡

በጭሪ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወጣት አርሶ አደሮች ከጥቁር እንጨት የተለያየ መድሃኒት እንደሚገኝ ወደ አካባቢው እየመጡ ምርምሩን የሚያካሄዱ ባለሙያዎች ሲናገሩ መስማታቸውን ይናገራሉ፡፡ እንዲሁም ቅርፊቱም ዶላር እንደሚያስገኝ መረዳታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ቀደም ሲል ስለ እንጨቱ የነበራቸው ግንዛቤ ቢበዛ ለቤት ምሰሶነት ከዛም በዘለለ ደግሞ ለማገዶነት የሚያገለግል መሆኑን ነው፡፡ አሁን ግን ልዩ አገልግሎት እንደሚሰጥ በመረዳታቸው ለሚደረገው የምርምር ሥራ የበኩላቸውን ድጋፍ ማድረግ ይፈልጋሉ፡፡ እነርሱም በማራባት ተጠቃሚ መሆን ይሻሉ፡፡

ከእነዚህ አርሶ አደሮች መካከል በዚሁ በጭሪ ቀበሌ ነዋሪ የሆነው ወጣት አርሶ አደር አብዱራሂም መሀመድ የጥቁር እንጨት አገልግሎት ጠንካራ በመሆኑ ለቤት ምሰሶነት እንደሚያገለግል ነው የሚረዳው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ሰው ለፈለገው አገልግሎት ሊያውለው እንደሚችል ያመለክታል፡፡ ወጣት እንደመሆኑም ዝርያውን አግኝቶ ቢያራባ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችልም ነው የገለጸው፡፡

በኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና እድገት ፕሮግራም ተባባሪ ዶክተር ዳኛቸው ሉሌ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ የሲናና ምርምር ማዕከል ቴክኖሎጂዎችን በማውጣት ወደአርሶ አደሩ የማድረስ ሂደትን ነው እየተከተለ ያለው፡፡

በፌዴራል ግብርና ምርምር በአሁኑ ወቅት እንደ አገር የፈለቁት በአጠቃላይ ከአንድ ሺ 200 ዝርያዎች በላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ውስጥ ድርሻ ካላቸው መካከል የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል አንዱ ሲሆን፣ የሚሰራው እህል ላይ ብቻ አለመሆኑን ዶክተር ዳኛቸው ይናገራሉ፡፡ ማዕከሉ ነባር እንደመሆኑ የተለያዩ ዝርያዎችን ለማፍለቅ የሚጥር እንደሆነም ያመለክታሉ፡፡

 ዶከተር ዳኛቸው እንደሚሉት፤ በባሌ ዞን ወደተለያዩ ቦታዎች ሲኬድ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ይገኛሉ፡፡ ወደ አጋርፋ፣ ጊኒር እንዲሁም ደሎ መና የሚታዩ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ሁሉ በዋናነት አርሶ አደሩን ብሎም አገሪቱን የሚጠቅሙ ናቸው፡፡ በመሆኑም በሲናና እየፈለቁ ያሉ ቴክኖሎጂዎች በመልካም እንቅስቃሴ ላይ የሚገኙ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

አርሶ አደሩም የሚፈልቁ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በቅድሚያ ሊተዋወቋቸው ይገባል የሚሉት ዶክተር ዳኛቸው፤ ግንዛቤ ካገኙና ከመረጧቸው በቀላሉ ወደትግበራው መግባት የሚችሉ እንደሚሆኑ ነው ተናገሩት፡፡ የአርሶ አደሩ ግንዛቤ ሲዳብር በሕይወቱ ላይ እንዲሁም በቀጣይ ትውልድ ላይም ለውጥ እንደሚያመጣ ይረዳሉም ሲሉ ነው ያብራሩት፡፡

አስቴር ኤልያስ

   

 

 

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አውሮፓ በዘመናት ታሪኳ አዲስና አይታው የማታውቀው የሕዝበኝነት (ፖፕሊስት) የፖለቲካ ንቅናቄ እየተስፋፋ በመሄዱ ጭንቀት ውስጥ ወድቃለች፡፡ ንቅናቄው አውሮፓ የምትመራበትን የሊበራል ርእዮተ ዓለም ሙሉ በሙሉ የማይቀበል ሲሆን፤ በአብዛኛው ሀገራትም ስር እየሰደደ የፖለቲካውን መንበረ ሥልጣንም እስከመያዝ ደርሷል፡፡ በፍጥነት በመስፋፋት ላይ ያለው የሕዝበኝነት ፓርቲዎችና ንቅናቄያቸው ወደምስራቅና ሰሜን አውሮፓም ተሸጋግሯል፡፡ የፖለቲካ ንቅናቄው በየሀገራቱ ሰፊ የሕዝብ ድጋፍና ይሁንታ ተቸሮታል፡፡ የቀድሞው የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ተቋም የሆነው ኢንስቲትዩት ፎር ግሎባል   ቼንጅ የተባለው ቲንክ ታንክ (ሃሳብ አመንጪ ተቋም) ባቀረበው ጥናት የሕዝበኝነት (ፖፕሊስት) የፖለቲካ ንቅናቄ እየተስፋፋ መሄድ ለዴሞክራሲ እውነተኛ አደጋ ነው፡፡

አውሮፓ የሊበራሉና የኒዮ ሊበራሉ ፖለቲካዊ ርእዮተ ዓለም የተቀረጸባት እምብርት ስትሆን፤  ዛሬ ደግሞ ሕዝብን እንወክላለን ለሕዝብ እንቆማለን የሚሉ በተለምዶ ፖፕሊስት (ሕዝበኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች) በብዛት እየተፈጠሩ ይገኛሉ፡፡ ይህ ዝንባሌም የባልቲክ ሀገሮችን ሙሉ በሙሉ ወደመሸፈኑ ደርሷል፡፡

ዩሮ ኒውስ ሕዝበኝነትን በተመለከተ በቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር የሚመራውን ተቋም ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ሕዝበኛነት ከሚታሰበው በላይ ርቆ  በአውሮፓ እየጎለበተ መጥቷል፡፡ ሪፖርቱ የሕዝበኝነት (ፖፑሊስት) ፓርቲዎች በበርካታ ሀገራት የመንግሥትን ሚዛን የሚደፋ ሥልጣን እየወሰዱ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል፡፡ ተቋሙ ጥናቱን ያደረገው እኤአ ከ2000  እስከ 2017 በ39 የአውሮፓ ሀገራት የ102 ሕዝበኛ ፓርቲዎችን የምርጫ ውጤት በማሰባሰብ ነው፡፡

የሕዝበኞቹ መነሳት በብዙ ሀገራት ማህበራዊና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች እንዲለወጡ  በማድረጋቸው እንስማማለን ይላል። የኢንስቲትዩት ፎር ግሎባል ቼንጅ ሪፖርት፡፡ የሕዝበኞቹ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በአውሮፓ ውስጥ ባሉ ብሔራዊ  መንግሥታት መካከል አዲስ ውጥረት ፈጥሯል፡፡ በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ በአንድ ወቅት የጎለበተ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ተደርገው በሚወሰዱት ላይ ግፊት ማሳደር መጀመራቸውን ይገልጻል፡፡

ሕዝበኝነት ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ አንስቶ መልስ የሚሰጠው ዘገባው  ሕዝበኝነት በፖለቲካው  ሥርዓት ውስጥ  በጣም መጠነ ሰፊ በሆነ መልኩ  በቀኝ አክራሪውም ሆነ በግራ አክራሪው ውስጥ ስር የሚሰድ ዝንባሌ መሆኑን ያመለክታል፡፡  ሕዝበኝነት በወዳጅና በጠላት መካከል ልዩ የሆነ መስመር ያሰምራል፡፡ ደጋፊዎቹ ሕጋዊ ሆነው ሲወሰዱ የሚቃወሙት ደግሞ በሕገወጥነት ይፈረጃሉ፡፡ ፓርቲዎቹና ፖለቲከኞቹ ኢፍትሀዊነትንና ሙስናን ከማውገዝ ይልቅ በተለያየ መልኩ የሕዝቡ ተወካይ ነን  በሚል  በፀረ ምሁራን፣ በፀረ ስደተኞች አቋም  ወይንም በአናሳዎች ላይ በተቃውሞ ይዘምታሉ፡፡ የሕዝበ ውሳኔ ፍቅር እንዳላቸውም ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡

ሦስት አራተኛ የሚሆኑት የአውሮፓ ሕዝበኛ ፓርቲዎች የቀኝ ክንፍ ፖለቲካ መስመር አራማጆች ናቸው፡፡ እንደ ጥናቱ ከ102 ውስጥ 74 ያህሉ የቀኝ ክንፍ ፖለቲካ መስመር አራማጆች ናቸው፡፡ ቢሆንም የግራ ክንፍ ሕዝበኛነት ደግሞ የደቡብ አውሮፓ ሀገራት ሉቴንያን ጨምሮ እጅግ በጣም ጠንካራ መሆኑን ጥናቱ ያሳያል፡፡

ጥናቱ ማዕከላዊና ምሥራቅ አውሮፓ ያልተጠበቀ የሕዝበኝነት ቀለበት የነገሠባቸው መሆኑን ያሳያል፡፡ ሕዝበኞች  በምሥራቅ አውሮፓ  በጣም ጠንካራ መሆናቸውንና ከፖላንድ እስከ ሜቄዶንያ ያለውን ቦታ ማካለላቸውን ይጠቁማል፡፡ ሕዝበኞች በሰባት ሀገራት ሥልጣን ይዘዋል፡፡ ከሁለት በላይ በሆኑ ሀገራት ደግሞ አነስተኛ ጥምረት አላቸው፡፡ አንዱ የጥናቱ  ሪፖርት አቅራቢ የሆነው ያስቻ ሙንክ «አሁን ከባልቲክ ጀምረህ በሁሉም መንገድ እስከ እስያ ድረስ አንድም ሳትተው በሕዝበኞች በሚተዳደሩ ሀገሮች ውስጥ እያለፍክ መንዳት ትችላለህ» ሲል በትዊተር ገጹ አስፍሯል፡፡

የቀኝ ክንፍ ፖለቲካ አራማጆች የሆኑት የፖላንዱ ሕግና ፍትህ ፓርቲ  እንዲሁም የሀንጋሪው ፊድዝ ፓርቲ በመሬት፣ በደምና በባሕል ላይ ተመርኩዘው ብሔራዊነትን በማራመዳቸው ሰፊ የሕዝብ ድጋፍና እጅግ ጠንካራ መሰረት ገንብተዋል፡፡ እነዚህ ሁለት ሀገራት ቁልፍ የዴሞክራቲክ ተቋማት የሆኑትን ነፃ ሚዲያና ነፃ ፍርድ ቤትን ከሥራ ውጪ አድርገዋል ሲል ጥናቱ ይገልጻል፡፡

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ሕዝበኞች (ፖፑሊስት) ፖለቲከኞች በምርጫ ወቅት ያገኙት ድምጽ በሦስት እጥፍ አድጓል፡፡ በ2017 በአማካይ ከ30 ፐርሰንት በላይ ደርሷል፡፡ በአውሮፓ ለምርጫ ተወዳዳሪነት የተሰለፉት ሕዝበኛ ፓርቲዎች ቁጥር ከሁለት እጥፍ በላይ አድጓል፡፡ የሕዝበኞቹ መንግሥታት ዋነኛ ተቀናቃኞች ራሳቸው ሕዝበኞች ናቸው ሲል ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡

ሕዝበኞች በምዕራብና በሰሜን ትርጉም ያለው ተቀባይነት አግኝተዋል፡፡ በምዕራብ አውሮፓ በአማካይ የነበራቸው 13 በመቶ  የድምጽ ድርሻ እኤአ በ2000 ከነበረው 4 በመቶ የበለጠ ነው፡፡ ሕዝበኞች መሬት የረገጠ ሥልጣን በኦስትሪያና በስዊዘርላንድ ይዘዋል፡፡ ከምሥራቁ በጣም ባነሰ ወሳኝነት ቢሆንም በፈረንሳይ ማሪን ሌፔን በጀርመን ኦልተርኔቲቭ ፎር ጀርመኒ (ኤኤፍዲ) ከፍ ብለው የሚታዩ ናቸው፡፡  

ትርጉም ባለው ደረጃ  እያሻቀበ ያለው  የቀኝ አክራሪ ሕዝበኝነት  ተጽእኖ  ማዕከላዊ ቀኝ ፓርቲዎች የስደተኞችን ጉዳይ በመሳሰሉት በጣም አክራሪ የሆኑ አቋሞችን እንዲወስዱ  ግፊትና ተጽዕኖ ማድረግ መቻላቸውን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡ ለዘብተኛ የሆኑ ፓርቲዎች  ቀድሞ በተለመደው ሁኔታ ባሕላዊ ጥምረት ለመመስረት አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል ብሏል ሪፖርቱ፡፡

የቀኝ ክንፍ ሕዝበኞች በዴንማርክና በስዊድን በፊንላንድና በኖርዌይ በመንግሥት ውስጥ ከተወከሉ ሕዝበኞች ጋር በመሆን ከፍተኛ ቁጥር ያለው የድምጽ ድርሻ በማግኘት አሸንፈዋል፡፡ ስደተኞችን በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ያላቸው ተጽዕኖ አድጓል፡፡ ይህም በአብዛኛው መንግሥታዊ ሥልጣን በሚጋሩባቸው የባልቲክ ሀገራት ውስጥ ከፍተኛ ስሜት እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ሪፖርቱ በደቡብ አውሮፓ የሚገኙት ሕዝበኛ ፓርቲዎች ወደ ግራ ያዘመሙ መሆናቸውን ያትታል፡፡

ሪፖርቱ ሲሪዛ በሥልጣን ላይ የሚገኙባትን ግሪክን እንዲሁም በስፔን  የተቃዋሚውን  ዋና አለት የመሰረተውን ፖዴሞስ  ፓርቲን ነጥሎ አውጥቷል፡፡ ግራ ዘመም ሕዝበኝነት በፈረንሳይ የምርጫ ውድድር ጂን ሉክ ሜሌንኮን በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለማሸነፍ በተቃረበበት ወቅት እንዲሁም በእንግሊዝ በሌበሩ ፓርቲ ተቃዋሚ አማካኝነት በተደረገው ውድድር ትርጉም ያለው ጉዞ ማድረጉን ያስረዳል፡፡

በኢጣሊያ የአምስት ኮከብ ንቅናቄ የሚባለው ቀኝ ወይ ግራ ዘመም ፖለቲከኛ የሆነው ፓርቲ  የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓቱን መሰረት በመገዳደር የበለጠ ፀረ ስደተኞች እየሆነ መምጣቱን ጥናቱ ገልጿል፡፡ ቢሆንም የብሌር ተቋም በአውሮፓ በአጠቃላይ ግራ ክንፍ ሕዝበኝነት በአንጻራዊነት ከግሪክና ከሉቴንያ በስተቀር በቀላሉ ሥልጣን ሊይዝ እንደሚችል  አስምሮበታል፡፡

ሕዝበኝነት በተግባር ለዴሞክራሲ አደጋ መሆኑን የሚገልጸው ሪፖርት ፀረ አውሮፓ ሕብረት፣ ፀረ ስደተኛ፣ ተከላካይ የሆኑ ሕዝበኛ ፓርቲዎች ዋናውን መስመር  የዴሞክራቲክ  ልምዶችን ሳይጥሱ የበለጡ ብሔርተኛ ወደሆኑ አቅጣጫዎች ለውጠዋቸዋል ይላል፡፡  ቢሆንም አብዛኛዎቹ ሕዝበኛ ፓርቲዎች ጥቂቶቹን በሥልጣን ላይ ያሉትን ጨምሮ  በጣም በጥልቀት ሊበራል ያልሆነ ፖሊሲን ይደግፋሉ፡፡ የሕዝብ ድጋፍን በመጠቀም የሕግ የበላይነትን በመርገጥ የአነስተኞችንም መብት ይጥሳሉ፡፡ በዴሞክራሲ በራሱ ላይ እውነተኛ የሆነ አደጋ ጋርጠዋል ይላል ሪፖርቱ፡፡

ሀንጋሪ በሚገርም ምሳሌነት ተጠቃሽ ናት፡፡ መንግሥቷ ወደ አነስተኛ  ፈላጭ ቆራጭነት ተሸጋግሯል የሚል ክስ ይሰማበታል፡፡ ፍርድ ቤቶችንና የምርጫ ኮሚሽኑን በታማኞች ሞልታለች፡፡ በነፃ ሚዲያውና በዩኒቨርሲቲዎች ላይ ጥቃት ትሰነዝራለች፡፡ የወደፊቱ ነፃና ግልጽ ምርጫም ጥርጣሬ ውስጥ ወድቋል ይላል ጥናቱ፡፡ የፖሊሽ ዴሞክራሲም በፊት ከነበረበት በጣም የሚሰበር አይነት ሆኖ ነው የሚገለጸው፡፡ አዲሱ መንግሥት በፍትሕ ላይ በተደረገው ማሻሻያ የሥልጣን መለያየትን ባለመቀበሉ ይከሰሳል ሲል ገልጿል፡፡

የወደፊቱ መጪ ጊዜ ጨለማ ይሆን ይሆን ? የሚል ጥያቄ የሚያነሳው የተቋሙ ሪፖርት ሕዝበኝነት ከመዳከም ይልቅ ርቆ ሄዷል የበለጠ የምርጫ ድል አግኝቷል ሲል ይከራከራል፡፡ ለእዚህም በኦስትሪያ የፍሪደም ፓርቲ በመንግሥት ውስጥ መገኘቱን ይጠቅሳል፡፡ በስደትና በማህበራዊ ደህንነት ላይ የተጣለው ገደብ  በሌላም ቦታ በተመሳሳይ ሊቀዳ ሊወሰድ ይችላል ይላል፡፡

የአውሮፓ ፖለቲካ በይበልጥ ወደብሔርተኛነትና ተከላካይነት እየሄደ በመሆኑ ፊንላንድ፣ እስቶኒያ፣ ዴንማርክ እና ኖርዌይ በሕዝበኞች ተጽእኖና ግፊት የተነሳ የፖሊሲ ለውጥ አድርገዋል፡፡ በምሥራቅ አውሮፓ ያሉት ሥዕሎች በእርግጠኝነት ወደፊት የጨለመ ሁኔታ እንደሚኖር ያሳያሉ፡፡ በሀንጋሪና ፖላንድ ሕዝበኞች ዴሞክራቲክ ተቋማትን በማውደማቸው ክስ ይሰማባቸዋል፡፡ ሪፖርቱ ግራ ክንፍ ሕዝበኞች በአውሮፓ የሆኑ ቦታዎች ላይ ሙሉ በሙሉ  ተቃራኒዎቻቸው የሆኑትን ምሥራቅ አውሮፓዎች ኮርጀው ፓርላማን ፕሬሱንና     ፍርድ ቤቶችን ማጥቃት መጀመራቸው  አስጨናቂ መሆኑን  ይገልጻል፡፡

ወንድወሰን መኮንን

Published in ዓለም አቀፍ
Thursday, 04 January 2018 16:28

“ሁለቱ - 29ኞች”

ከተማዋ አለወትሮዋ ደምቃለች፡፡ የአየር ፀባዩም ከደጋ እና ወይናደጋ ለመጡት የከተማ ታዳሚዎች ብዙ አላስቸገረም፡፡ የሰው ልጅ መገኛ፣ የተለያዩ የቱሪስት መስህብ ባለቤቷ እና የአፋር ክልል ዋና ከተማ ሰመራ በህዳር ወር 2010 ዓ.ም፣ የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ያደረጉ የተለያዩ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ተቋማትን ግንባታ ወደ ሥራ በማስገባት ውበቷ ጨምሯል፡፡

የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ም/ቤት፣ የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት እንዲሁም የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ምስጋና ይግባቸው እና፣ “በሕገ-መንግሥታችን የደመቀ ሕብረ-ብሄራዊነታችን ለህዳሴያችን”!!  በሚል መሪ ቃል ለ12ኛ ጊዜ በአፋር - ሰመራ ከተማ የተከበረው የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ከታደሙት አንዱ ነበርኩኝ፡፡ ዋናው በዓል ህዳር 29 ከመከበሩ በፊት በነበሩት ቀናት የተለያዩ በርካታ ፍፃሜዎች/events/ ተከናውኗል - በሰመራ፡፡ ከእነዚህ አንዱ ህዳር 28/2010 ዓ.ም. የተደረገው ሲምፖዚየም ተጠቃሽ ነው፡፡ የህዳር 29 ትሩፋት የሆነው እና ሰመራ ከተማን የዘመናዊ ታላቅ ህንፃ ባለቤት እንድትሆን ባደረገው በዚሁ አዲስ አዳራሽ በተካሄደው ሲምፖዚየም በሁለት ምሁራን ማለትም አቶ ዓለማየሁ እርቅይሁን እንግዳ እና አቶ ጋሻው መሐመድ ሞትማ ተዘጋጅቶ የተፃፈው “ዋለልኝ መኮንን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ መሪ” የሚል መጽሐፍ በ100 ብር ተሽጧል፡፡ እኔም መጽሐፉን ገዝተው ካነበቡት አንዱ ለመሆን በቅቻለሁኝ፡፡ በዚህ አጋጣሚ በአራቱም መዓዘናት ያሉት የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ በዋነኛነት ወጣቱ መጽሐፉን ገዝቶ ቢያነበው በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም የዴሞክራሲ ኃይሎች የትግል ታሪክ በአግባቡ ሊረዳ ይችላል የሚል ሙሉ እምነት እንዳለኝ ስገልፅ ድፍረት አይሆንብኝም፡፡

ተጨባጭ ማስረጃዎችን አሰባስቦ በግልፅ የአማርኛ ቋንቋ የተቀነባበረው ይኸው “ዋለልኝ መኮንን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ መሪ” የሚለው መጽሐፍ፣ በርካታ ቁምነገሮች የዳሰሰ ቢሆንም የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ግን በአንድ ጉዳይ ላይ ብቻ ትኩረት አድርጓል፡፡ ይኸውም አሁን ላለችው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ መመሥረት አንኳር ጉዳይ በሆነው ማለትም፤ በአጠቃላይ በ1959 ዓ.ም. በተመሠረተው የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማህበር /National union of Ethiopian University students/ ውስጥ ስር-ነቀል /Radical/ ለውጥ ፈላጊና ተራማጅ አስተሳሰብ የነበራቸው እነ ዋለልኝ እና ጥላሁን ግዛው የወቅቱ የኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት ያደረጉት ተጋድሎ፣ /በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማህበር ለዘብተኛ እንዲሁም ስር ነቀል ለውጥ ፈላጊው እና ተራማጅ የሚባሉ ተማሪዎች ያቀፈ እንደነበረ ልብ ይሏል/ በዋነኛነት ደግሞ ስር ነቀል ለውጥ ፈላጊው እና ተራማጁ ምሁሩ ታጋይ የህዝብ ልጅ ዋለልኝ መኮንን በኢትዮጵያ የብሄርና ብሄረሰቦች ጥያቄ የነበረው የማያወላዳ ዓቋም ምን ይመስል እንደነበረ በደምሳሳው ለማስታወስ እና አሁንስ ምን ይደረግ የሚል ነገር በአጭሩ ለመጠቆም ነው፣ የዚህ ጽሑፍ አጠቃላይ መነሻና መድረሻ፡፡

በአጠቃላይ መልኩ ሲታይ ስር ነቀል ለውጥ ፈላጊና ተራማጅ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በወቅቱ በኢትዮጵያ የነበሩ ዘርፈ ብዙ መሠረታዊ ችግሮች ማለትም፣ ፊውዳላዊ ሥርዓቱና የመሳፍንት ገዥ መደብ በዓርብቶ አደሮች እና በአርሶ አደሮች ሲያካሂድ የነበረው አስከፊ ጭቆና፣ የመሬት ላራሹ ጉዳይ፣ የትምህርት ሥርዓትና ኢ-ፍትሃዊ ተደራሽነት፣ የማህበረ-ኢኮኖሚ ችግሮች፣ የፖለቲካ ነፃነት ጉዳይ፣ የጾታ እኩልነት፣ የሴቶች ጭቆና እና በትግል ወቅት የሴቶች ተሳትፎ፣ የቋንቋና የባህል የበላይነትና የበታችነት ሁኔታ፣ በአጭሩ የብሄሮችና ብሄረሰቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጉዳይ መሠረታዊ መፍትሄ የሚሹ መሆናቸው በአግባቡ ተገንዝበው ይታገሉ ነበር፡፡

“ከስር-ነቀል ለውጥ ፈላጊና ተራማጅ ተማሪዎች መካከል በኢትዮጵያ የብሔር ጥያቄ ችግሮችንና ፖለቲካዊ መፍትሄዎችን በመያዝ በአደባባይ ደፍሮ ለውይይት የቀረበው ዋለልኝ መኮንን ነበር፡፡ በዚህ አቋሙ ሀገሪቱ ከተዘፈቀችባቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች ውስጥ የብሄር ጥያቄ አንዱ መሆኑን ስለተገነዘበ ጉዳዩን ከድብብቆሽ ወሬ በግልጽ ለውይይት ወደ አደባባይ አቅርቦታል፡፡”

ይኸውም “የብሄር ጥያቄ በኢትዮጵያ” “ON THE QUESTION OF NATIONALITIES IN ETHIOPIA” በሚል ርዕስ ዋለልኝ መኮንን ያቀረበው ጽሑፍ በብዙ ተማሪዎችና በሀገሪቱ ሕዝቦች ላይ አዲስ ስሜትን ፈጥሯል፡፡ በኅዳር ወር 1961 ዓ.ም. ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በልደት አዳራሽ በተዘጋጀው የ“እንኳን ደህና መጣችሁ” ፕሮግራም ላይ ዘውዳዊው የንጉሠ ነገሥቱ ሥርዓት በብሄሮች የማንነት ጥያቄ ዙሪያ ያሳደረውን ተጽዕኖ፣ በብሔሮች ነባራዊ ሁኔታና ወደፊት ሊሆን በሚገባው ፖለቲካዊ መፍትሔ ላይ ያተኮረ ጽሑፍ ዋለልኝ መኮንን ለውይይት አቅርቧል፡፡ ሰፊ የሆነ ውይይትና ክርክር ከተካሄደ በኋላም ጽሑፉ በ“ታገል” (Struggle) ይባል የነበረው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መጽሔት ላይ ታትሞ ወጥቷል፡፡

ዋለልኝ በዚህ ጽሑፉ ኀብረ ብሔራዊነትን በማንጸባረቅ ኢትዮጵያ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝብ ሀገር ብቻ ሳትሆን ከደርዘን በላይ የሆኑ ብሔሮች ማለትም ትግሬዎች፣ ኦሮሞዎች፣ አደሬዎች፣ ሶማሌዎች፣ ወላይታዎች፣ ጉራጌዎች፣ ወዘተ የሚኖሩባት፣ የየራሳቸውን ቋንቋ፣ እምነት፣ ባህል፣ የማኀበረሰብ ዕሴቶች በውስጧ አቅፋ የያዘች መሆኗን በግልጽ ወደ አደባባይ ለውይይት ያቀረበ በመሆኑ ሁሌም በታሪክ ተጠቃሽ ያደርገዋል፡፡

“መብታቸውን ለማስከበር ጥያቄ የሚያነሱ ብሔሮች ‘ጎሰኛ’ የሚል ቅጽል ስም ይሰጣቸዋል፡፡ እኔ ግን ብሔርተኛ ተብዬ መጠራትን እመርጣለሁ፡፡”  በማለት የማንነት ጥያቄን ማንሳት የጠባብነትና የጎሰኛነት አስተሳሰብ አለመሆኑን አስገንዝቧል፡፡ ዋለልኝ ይህንን ጽሑፍ በአደባባይ ለክርክርና ለውይይት ከማቅረቡ በፊት ስለብሔር ጥያቄና ፖለቲካዊ መፍትሔ ደፍሮ በግልጽ ለውይይት ያቀረበ አካል አልነበረም፡፡

ከላይ ካለው የስር-ነቀል ለውጥ ፈላጊውና ተራማጅ ምሁሩ ዋለልኝ መኮንን ጽሑፍ ማለት የሚቻለው፣ ዋለልኝ መኮንን የነበረውን ወቅታዊ ሃገራዊ ሁኔታ ከዓለም አቀፍ ጉዳዮች ጋር አገናዝቦ የመተንተንና መሠረታዊ ችግሮች የማየትና መፍትሄ የማስቀመጥ የፖለቲካ ብቃት፣ ህዝባዊ ወገንተኝነት፣ የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት መሆናቸው፣ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ልትቀጥል ከሆነም ህብረ-ብሄራዊነት(Nation-state) በአግባቡ ሥራ ላይ መዋል እንዳለበት ዋለልኝ መኮንን እና የትግል አጋሮቹ የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉለትን ዓላማ፣ ባለፉት 27 ዓመታት በሃገራችን ተግባራዊ ሆኖ፣ ተጨባጭ ፍሬ እያፈራ መሆኑ ሲታይ፤ ዋለልኝና ጓዶቹ በኢትዮጵያ ታሪክ ለዘለዓለሙ ህያው ሆነው እንደሚኖሩ በጉልህ የሚያሳይ ነው፡፡ እዚህ ላይ ሳይገለፅ የማይታለፍ ጉዳይ አለ፡፡ ይኸውም የዋለልኝ መኮንን የፖለቲካ ብቃቱና  ሰፊ የአተናተን አድማሱ ብቻ ሳይሆን ምን ያህል መጽሐፍ አንባቢ እንደነበረ እና የእንግሊዝኛ ቋንቋ አዋቂነቱ ምን ያህል ጥልቅ እንደነበር የሚያመለክት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ከዚህ ሁላችንም በተለይ ወጣቱ ትውልድ መጽሐፍ የማንበብ ባህል ማሳደግ ከእነ ዋለልኝ መኮንን ተሞክሮ ቢወስድ የአስተሳሰብ አድማሱን አስፍቶ ከስሜታዊነትና አጉል እልህ ተላቆ ምክንያታዊ አስተሳሰብ(Rational thinking) እንዲያዳብር እገዛ ያደርግለታል ቢባል ሃቁን መናገር እንጂ ክፋት አይኖረውም፡፡

ስር-ነቀል ለውጥ ፈላጊውና ተራማጁ ዋለልኝ መኮንን ለውድ ህይወቱ ሳይሳሳ ብዕርና ወረቀት ብቻ ይዞ ጨቋኙን ፊውዳል የኃይለሥላሴ ሥርዓት ዕድሜ እንዲያጥር ታሪክ የማይረሳው ገድል ፈፅሞ ክቡር መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ ይኸውም ዋለልኝ መኮንን እየታሰረና እየተፈታ በሀገር ውስጥ ይካሄድ የነበረውን ትግል በቁርጠኝነት እየመራ ከቆየ በኋላ ትግሉን ለማስቀጠል የሚያስችለውን የትግል ስልት በመቀየስ እንዲሁም በብሄር ጥያቄ ላይ ተመሳሳይ አቋም ከነበረው እና “የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ድርጅት” የሚል የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት ዝግጅት ላይ የነበረውን በአልጄሪያ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ቡድን፣ ያደረገለትን ግብዣ ተቀብሎ፣ ከሌሎች ስድስት/6/ የትግል አጋሮች ጋር በመሆን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መስመር ቁጥር 720 ቦይንግ ጄት አውሮፕላን ዕለተ ዓርብ ህዳር 29/1965 ዓ.ም. ጠልፈው ለ15 ደቂቃ አየር ላይ ከተጓዙ በኋላ፣ አብራቸው ከነበረች ታደለች ኪዳነ-ማርያም በስተቀር፣ ዋለልኝ መኮንንን ጨምሮ ስድስቱ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት በአፄ ኃ/ሥላሴ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተኮሱባቸው ጥይት የህይወት መስዋእትነት ከፍለዋል፡፡ ህዳር 29/1965 ዓ.ም. ከዋለልኝ ጋር መስዋዕት የከፈሉት ቆራጥ ታጋይ የህዝብ ልጆች፤ 1.ማርታ መብራህቱ 2.በላይ ታደሰ/መሐመድ ዑስማን መሐመድ/ 3.ጌታቸው ሃብቴ  4.ተስፋዬ  በርጋ  5.ዮሐንስ ፈቃዱ የተባሉ ናቸው፡፡

ከእነ ዋለልኝ መኮንን ቀደም ባሉት ዓመታት ማለትም “የቀድሞ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ/የአሁኑ የአዲስ አበባ/ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት እና የስር ነቀል ለውጥ ደጋፊ የነበረው ተማሪ ጥላሁን ግዛውም ታህሣሥ 18 ቀን 1961 ዓ.ም. በአፋኙ የኃ/ሥላሴ ሥርዓት ወታደሮች በተተኮሰ ጥይት ለሀገሩና ህዝቡ ክቡር መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ የጥላሁን ግዛው ደቀመዛሙርት የነበሩት እና የጥላሁን ግዛውን መገደል ተከትሎ በተቃውሞ ከተሳተፉት መካከል አበበ በርሀ፣ ስብሃቱ ውብነህ፣ ጀማል ያሲን የተባሉት አንጋፋ ታጋይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በአፄ ኃ/ሥላሴ መንግሥት ክብር ዘበኛ በተባለው ጦር ጥይት በደረሰባቸው ጭፍጨፋ ታሪክ የማይረሳው መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉት ተማሪዎች ደግሞ ቆስለዋል፡፡

ከእነ ዋለልኝ እና ጥላሁን በፊት በነበሩት ዓመታትም፣ የፊውዳላዊውን የአፄ ኃ/ሥላሴ ሥርዓት በመቃወም፣ የትግራይ ቀዳማይ ወያኔ አመፅ እና የጎጃም አርሶ አደሮች ፀረ-ምዝበራ የተቃውሞ እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም የባሌ፣ የጌዴኦ ወዘተ ህዝቦች የፀረ-ብሄራዊ ጭቆና ትግሎች በተካሄዱባቸው ወቅቶች ከፍተኛ የህይወት መስዋዕትነት ተከፍለዋል፡፡

 

 

ከታጋይ ሓዱሽ ካሡ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Published in አጀንዳ
Thursday, 04 January 2018 16:23

ተገቢ ውሳኔ

ኢህአዴግን ልብ ብሎ ላጤነው አስገራሚም አስደማሚም የሆነ የፖለቲካ ድርጅት ነው። ድርጅቱ በትክክልም በህዝብ ደምና በህይወት መስዋዕትነት የተፈጠረ፤ ይሄንንም ጠንቅቆ የሚያውቅ ለህዝብ ክብር ያለው ባለታሪክ ድርጅት ነው። ኢህአዴግ ህዝባዊ ድርጅት ነኝ ሲል በእርግጥም ህዝባዊነቱን የሚመሰክሩ በርካታ እማኞች ያሉት ፓርቲ ነው። ሁሉንም ትተን የሰሞኑን ሁኔታ እንኳን ብንመለከት ሀሳቡ ትክክል መሆኑን መረዳት ይቻላል።

ለ17 ቀናት በዝግ ስብሰባ የቆየው የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በስብሰባው መቋጫ አሁን በአገሪቷ  እየተፈጠሩ ላሉ ችግሮች ሃላፊነቱን እንደሚወስድ የገለጸውና ይቅርታ የጠየቀው በዚህ መንገድ ነበር፤ 

“ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው መላ የአገራችን ህዝቦች በከባድ ተጋድሎአቸው ያስመዘገቡዋቸውን ድሎች ጠብቆና አስፍቶ ለማስቀጠል ባለመቻሉ፤ እንዲሁም በድርጅታችን ውስጥም ሆነ በአገራችን ውስጥ የሚታዩ ልዩ ልዩ ችግሮችን በጊዜና በከፍተኛ የሃላፊነት መንፈስ ለመፍታት ባለመቻሉ ለደረሰው ጉዳት ሙሉ ሃላፊነቱን ከመውሰድ በተጨማሪ ለመላ የአገራችን ህዝቦችና የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎችን ልባዊ ይቅርታ ይጠይቃል። …አሁን በአገራችን የሚታየውን ሁኔታ እንደሚያስተካክልና የድል ጉዞውን እንደሚያስቀጥልም ቃል ይገባል”።

ይህ የዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አንድ መገለጫ ነው። ለመሆኑ በኢትዮጵያ ታሪክ በዚህ ደረጃ መንግሥት ሆኖ ይቅርታ የጠየቀ መንግሥት ይኖር ይሆን? በጭራሽ! ኢህአዴግ ግን የይቅርታ ባህል ያለው ፓርቲ በመሆኑም ጭምር ይመስላል ህዝብን ይቅርታ ጠይቋል። ተመሳሳይ ጥፋት ላለመፈጸምም ቃል ገብቷል፡፡ ይሄንን ማድረግ በእርግጥም ህዝባዊነት ነው። ይሄንን ለማድረግ ደግሞ ኢህአዴግ መሆንን ይጠይቃል። ምክንያቱም ገዥም ፓርቲ ይሁን ተፎካካሪ ፓርቲ  በዚህ ደረጃ አደባባይ ወጥቶ ይቅርታ ሲጠይቅ አልታየምና ነው።

ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ገብተው የነበሩ አገራት ታሪክ የሚነግረን አሁን ኢህአዴግ እያደረገ ካለው በተቃራኒው ነው። አገራቱ በተመሳሳይ ችግር ውስጥ ገብተው በነበሩባቸው አጋጣሚዎች የገዥ ፓርቲ አመራሮች እግሬ አውጭኝ ብለው አገር ጥለው ሲሄዱ፣ በተፈጠረው ችግር የለሁበትም ብለው በሌሎች ላይ ሲጠቆሙ እና ሌላም ሌላም ሌላም ከደሙ ንጹህ ነኝ ተግባራትን ሲፈጽሙ ነው የታዩት። ኢህአዴግ ከዚህ ነጻ ነው። እንዲያውም ቀደም ብለው ከድርጅት ሃላፊነት የተሰናበቱ ከፍተኛ አመራሮችን ሳይቀር ወደራሱ መልሶ አገርና ህዝብን ለመታደግ ቃል ገብቷል። 

ኢህአዴግም እንደ ኢህአዴግ እርስ በርሱ በሃሳብ ልዩነት ተፋጭቶ አበቃለት ተብሎ በወዳጅም በጠላትም ተነግሮበት ሲያበቃ፤ ችግሩ ወደ ውጭ መውጣት ሲጀምር መልሶ አንድ እንደሚሆን፤ እንዲያውም ከቀደመው የበለጠ ጥንካሬ ይዞ ብቅ እንደሚል በተለያዩ ወቅቶች ታይቷል። ሌላው ሌላው ቀርቶ የ1993 ዓ.ም ድርጅቱን ክፍፍልና የድህረ ምርጫ 97 ብሎም የአምናውን ሁከት መመልከት ብቻ በቂ ነው። እነዚህ ወቅቶች የኢህአዴግ ህዝባዊ ፓርቲነት የተፈተኑበት አጋጣሚዎች ናቸው። ኢህአዴግ ግን ፈረሰ ሲሉት ታድሶ፤ አበቃለት ሲባል እንደ አዲስ አንሰራርቶ ይሄንን አገር ከድህነት አረንቋ እያወጣ፣ የዴሞክራሲ መሰረትን እያጸና፣ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን እያጎለበተ፣ አገሪቷን ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገረ ይገኛል። በችግር ወቅት አንድ መሆንና ያንን ችግር ማለፍ የዚህ ድርጅት ልዩ ባህሪ የሆነም ይመስላል። ያም ሆኖ ግን ካለፈው ተምሮ ዳግም ወደ ችግር እንዳይገባ ከገባም በፍጥነት ማረም ከአንድ ህዝባዊ ፓርቲ የሚጠበቅ ተግባር ነውና ኢህአዴግ በዚህ ባህሉ ሊገፋበት ይገባዋል።  

የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከስብሰባው ማግስት እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች ይበል የሚያስብሉ ናቸው።  በአንድም በሌላም ጥፋት በህግ ጥላ ስር ሆነው የቆዩ ፖለቲከኞችን በይቅርታ ለመፍታት መወሰኑ የዚህን ድርጅት ይቅር ባይነትና ቀደም ሲልም ህዝቡን የጠየቀው ይቅርታም ከአንጀት እንጂ ከአንገት አለመሆኑን ያሳያል። ይህ ለአገራችን ፖለቲካ ይበል የሚያሰኝ ታላቅ ውሳኔ ነው። በዚህ ውሳኔ አገር ይደሰታል፤ ህዝብ ይረካል፤ ኢህአዴግም ብዙ ያተርፋል። በተቃራኒው አገሪቷ አበቃላት፤ ስርዓቱም ወደቀ ሲሉ ለነበሩ ወገኖች አናዳጅና አሳባጅ ውሳኔ ነው። ምክንያቱም ይህ አገር እና ህዝብ እንዲፈርስና እንዲወድቅ ከፍተኛ በጀት መድበው እየሰሩ ናቸውና ውሳኔው ትልቅ ኪሳራ አምጥቶባቸዋል።

አሁን ተራው ይቅርታ የተደረገላቸው ፖለቲከኞች ነው። የተደረገላቸውን ምህረት በአግባቡ ተጠቅመው ይሄንን አገርና ህዝብ ሊጠቅም በሚችል መንገድ ብቻ መጓዝ ይጠበቅባቸዋል። ይሄንን አለማድረግ ዳግም የህግ ተጠያቂነት ሊያስከትል እንደሚችል ልብ ሊሉት ይገባል። አሁን ጊዜው የሥራ ነው እንጂ የሴራ አይደለምና ሁሉም ወገን አንድ አካል አንድ አምሳል ሆኖ አገሪቷን ወደፊት ሊያራምድ የግድ ይላል።

Published in ርዕሰ አንቀፅ

አቶ ዳምጤ ቦጋለ በምኒልክ ሆስፒታል የዓይን ህክምና ለማግኘት ቢመላለሱም በወረፋ መብዛት ምክንያት በአፋጣኝ አገልግሎት ማግኘት ተቸግረው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በሆስፒታሉ በማታ ክፍለ ጊዜ የህክምና አገልግሎት መሰጠት በመጀመሩ በወረፋ ምክንያት ዘግይቶ የነበረውን ህክምና በቀላሉ እንዳገኙና ጤናቸውም እንደተመለሰ ይገልፃሉ፡፡

በሆስፒታሉ የሚሰጠው የማታ ክፍለ ጊዜ ህክምና ተገልጋዩን ተጠቃሚ እያደረገ ቢሆንም፤ በቀን ክፍለ ጊዜ የሚሰጠውን አገልግሎት እንዳያስተጓጉለው ስጋት አላቸው፡፡ አንዳንድ የህክምና ባለሙያዎች በቀን ለመታከም የሚመጡትን ህሙማን በማታው ክፍለ ጊዜ መጥተው እንዲታከሙ ማድረጋቸውን የሚናገሩት አቶ ዳምጤ፤አግባብ አለመሆኑንና የሆስፒታሉ አስተዳደር ጥብቅ ክትትል ማድረግ እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡

ነዋሪነታቸው በአራዳ ክፍለከተማ ወረዳ 7 የሆኑት ወይዘሮ የሺወርቅ አለሙ፣ በምኒልክ ሆስፒታል በማታው ክፍለ ጊዜ ህክምናቸውን ሲከታተሉ ነበር፡፡ እንደእሳቸው አባባል፤ በሆስፒታሉ በማታው ክፍለ ጊዜ በተመጣጣኝ ክፍያ የሚሰጠው ህክምና ታካሚውን ከእንግልት አድኖታል፡፡ በግል ክሊኒክ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ህክምናዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ በሆስፒታሉ በመሰጠታቸው እርሳቸውና ሌሎች ታካሚዎች የሚፈልጉትን አገልግሎት እንዲያገኙ አድርጓል፡፡

በማታ ክፍለ ጊዜ የሚሰጠው የህክምና አገልግሎት፣ ቀን ላይ ካለው ወረፋ የተሻለ ቢሆንም፤ የህክምና ባለሙያዎች ከቀን ይልቅ ማታ ላይ ትኩረት እያደረጉ በመሆኑ የቀን ታካሚዎች እንዳይጉላሉ የአሰራሩ አተገባበር ላይ ያላቸውን ስጋት እርሳቸውም ያነሳሉ፡፡ የሆስፒታሉ አስተዳደርም በሁለቱ ፈረቃ የሚሰጠው ህክምና ተገልጋዩን ያማከለ እንዲሆን ማድረግ እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡

የማታ ክፍለ ጊዜ የህክምና አገልግሎት ባለሞያዎችን በመንግስት የህክምና ተቋማት የማቆየት፣ ታካሚዎች በመረጡት ባለሙያ አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ የማድረግና ተቋሞቹ የውስጥ ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ የማድረግ ዓላማ ይዞ ነው በ2004 ዓ.ም የተጀመረው፡፡ አገልግሎቱ በህክምና አሰጣጡ ላይ የፈጠረው የአገልግሎት መሻሻል እንዳለ ሆኖ ከተገልጋዮችም ከህክምና ባለሞያዎችም ቅሬታ እየተነሳበት ይገኛል፡፡

የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ሽመልስ ሰለሞን፣ በማታው ክፍለ ጊዜ አብዛኛው የህክምና ክፍሎች አገልግሎቱን እየሰጠ እንደሆነና በተለይ የአይን ህክምና ክፍል ከፍተኛ ተገልጋይ እንዳለው ይናገራሉ፡፡ ከመደበኛ ሰዓት ውጭ የሚሰጠው አገልግሎት የተጀመረበት ዓላማዎች ከማሳካት አኳያ ገቢያቸው የተሻለ እንዲሆን በማድረጉ ከፍተኛ ባለሙያዎች  ሆስፒታሉን እንዳይለቁ እንዳደረገና በተጨማሪም አገልግሎቱ  ለታካሚው የሚሰጠውንም አማራጭ እንዳሰፋና ሆስፒታሉም የውስጥ ገቢውን እያሳደገ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረጉን ይጠቁማሉ፡፡

‹‹ታካሚዎችን ከመደበኛው አገልግሎት ወደ ማታው ክፍለ ጊዜ የመግፋት እና በማታው ክፍለ ጊዜ ምርመራ በማድረግ ውጤቱን በመደበኛ ሰዓት አገልግሎት የመስጠት ሁኔታ አለ የሚል ቅሬታ በአንድ የህክምና ክፍልና አንድ የህክምና ከፍተኛ ባለሙያ ላይ ደርሶ ከፍተኛ ባለሙያን ከማታው የህክምና አገልግሎት እንዲታገድ አድርገናል›› ብለዋል፡፡

ዶክተር ሽመልስ፣ የማታው መርሃ ግብር የሚገኘውን ገቢ ከፍተኛ ድርሻ ለባለሙያዎች ቢሰጥም፤ ‹በዓይን ህክምና ላይ ያለው ክፍያ በምንጠብቀው ልክ አይደለም፡፡ ከሥራ ሰዓት ውጪ እዚህ ከምናገለግል ይልቅ የግል ተቋማት ጋር ብንሰራ የበለጠ ተጠቃሚ እንሆናለን፡፡ ከምናገኘው ገቢ ላይ ሁለት ጊዜ የሚቆረጠው ታክስ ከፍተኛ ነው› በሚል ቅሬታ ምክንያት ራሳቸውን ከአገልግሎቱ ያገለሉ ከፍተኛ የዓይን ባለሙያዎች መኖራቸውን ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹በቀጣይ መመሪያውን በመከለስ የባለሙያዎች ቅሬታ ሊታይ የሚችልበት መንገድ እስካልተፈጠረ ድረስ ባለሙያዎቹን አሁን ባለው ሁኔታ ወደ አገልግሎቱ ለመመለስ አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጥሯል›› ብለዋል፡፡

እንደ ዶክተር ሽመልስ ገለጻ፤ አገልግሎቱ በከፍተኛ የህክምና ባለሙያዎቹ ላይ የፈጠረው ቅሬታ በርካታ ቁጥር ያላቸው ታካሚዎች እንዲጉላሉ እያደረገ ነው፡፡ ታካሚዎች የሚፈልጓቸው ከፍተኛ የህክምና ባለሙያዎች በአገሪቱ ጥቂት በመሆናቸውና በማታው ክፍለ ጊዜ ታካሚዎችን ባለማከማቸው መደበኛው ስራ ላይ ጫና ፈጥሯል፡፡ በድጋሚ በመደበኛ ሰዓት ላይ ያለው ወረፋ እንዲበዛ አድርጓል፡፡

ባለሙያዎቹ የሚያነሱት ቅሬታ ሊፈታ የሚችለው በከፍተኛ ውሳኔ ሰጪዎች ቢሆንም፤ የሆስፒታሉ አስተዳደር ግን እንደመፍትሄ  እየሰራ ነው ያለው፤ ባለሙያዎቹ የህብረተሰቡን እንግልት ታሳቢ በማድረግ በማታው ክፍለ ጊዜ እንዲሰሩ የመነጋገር እና ቅሬታቸውን በተለያዩ መድረኮች ላይ ለማንሳት እየሞከሩ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

አገልግሎቱ ያለውን ጠቀሜታ የበለጠ ለማጉላት መፍትሄ ያሉትንም ጠቁመዋል፡፡ ባለሙያዎቹን የማያሰሩ መመሪያው ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን መከለስ እና የሆስፒታል አስተዳደር ደግሞ የተገልጋዩንና የባለሙያውን ጥያቄ መሰረት ባደረገ መፍትሄ ለማምጣት በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅበትም ያመለክታሉ፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የክሊኒካል አገልግሎት ተወካይ ዳይሬክተር ዶክተር ይበልጣል መኮንን በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ አገልግሎቱን የተወሰኑ ጤና ተቋማት ብቻ በመጀመራቸውና ያቋረጡም ስላሉ አገልግሎቱ በስፋት እየተሰጠ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ሆስፒታሎቹ መጀመሪያ የወጣው መመሪያ ላይ በ2007 ዓ. ም ማሻሻያ ቢደረግም፤ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ የሚያደርጉ ተቋማት ግን የሉም፡፡ ከማታው ክፍለ ጊዜ የሚገኘው ገቢ 85 በመቶው ለባለሙያዎቹ፣ 15 በመቶ ደግሞ ለተቋሙ እንዲከፋፈል መመሪያው ቢያዝም፤ አንዳንድ ሆስፒታሎች ግን ከሆስፒታሉ ቦርድ ጋር ተነጋግረው የክፍያ ዋጋውን ከተተመነው በላይ ሲጨምሩ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ የሆስፒታሉን ድርሻ ከ15 ወደ 10 በመቶ የመቀነስና በባለሙያዎች መካከል ያለውም የገንዘብ ክፍፍል ግልጽ ያለመሆን ሁኔታዎች አሉ፡፡

በመደበኛ አገልግሎት ማከም እየተቻለ ወደ ማታው መርሃ ግብር ማሸጋገር፣ የገቢ ክፍፍል ግልፅ ያለመሆንና በጤና ተቋሞቹ የዳሰሳ ጥናት ባደረጉበት ወቅት ያገኙት መሆኑን ጠቅሰው፤ አገልግሎቱ ውስንነቶች ቢኖሩትም ዓላማውን በትክክል ማሳካቱን ጠቁመዋል፡፡ እንዲሁም በጤና ተቋማቱ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ባለሙያዎችንና ታካሚዎችን በመጠየቅ በተገኘ ምላሽ የተለዩ ዋና ዋና ችግሮች እንዳሉና በዳሰሳ ውጤት መሰረት መመሪያው እንደተከለሰ አመልክተዋል፡፡ የመመሪያ ክለሳ ስራውም የማጠቃለያ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ዶክተር ይበልጣል እንደሚያስረዱት፤ የተሻሻለው መመሪያ በዋናነት የመደበኛና የማታውን ክፍለ ጊዜ አሰራርን የሚለይ ነው፡፡ የማታ ክፍለ ጊዜውን ለብቻ የሚያስተዳድር ተጠሪ ባለሙያ ያስፈልጋል፡፡ ተጠሪ ባለሙያው የመደበኛ ህክምና አሰጣጡ ላይ ምንም አይነት ጫና እንደማያሳድር የሚታወቀው በማታው ክፍለ ጊዜ የሚሰጠው አገልግሎት ከመደበኛው ጋር ሲነፃፀር ነው፡፡

በተሻሻለው መመሪያ መሰረት ተጠሪ ባለሙያ ያስፈለገው የአገልግሎቱን ገቢ በትክክል ለማስተዳደር ነው፤ በአገልግሎቱ የሚገኘው ገቢ በትክክል መከፋፈሉን እንዲሁም በግልጽ እንዲሰራ የሚቆጣጠር ባለሙያዎችን ለመመደብ ነው፡፡ የማታው ክፍለ ጊዜ አገልግሎትን በመደበኛ ኃላፊነት የሚይዝ ባለሙያ ሲመደብ የአገልግሎት መረጃ አያያዝና አሰራር ላይ ያሉ ችግሮች ይቃለላሉ፡፡

ዜና ሐተታ

ሰላማዊት ንጉሴ

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።