Items filtered by date: Friday, 05 January 2018

           አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ወይም የፈጠራ ውጤቶች የሰዎችን አኗኗር ለማቅለል የጎላ ጠቀሜታ እንዳላቸው ይታመናል፡፡የዘርፉ ባለሙያዎችም በአቅራቢያቸውና በዙሪያቸው የሚያስተውሏቸውን በተለይም በዕለት ተዕለት ኑሮ ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን የሚፈቱ የፈጠራ ሥራዎቻቸውን እነሆ በማለት እያገዙ ይገኛሉ፡፡ይሁን እንጂ የቴክኖሎጂ ዘመን በሚባልበት በዚህ ወቅት የቴክኖሎጂ ተቋዳሽ ያልሆኑ አካባቢዎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡በተለይም እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች ቴክኖሎጂ ገና ነው፡፡በገጠሩ ደግሞ ቴክኖሎጂውን መጠቀም ቀርቶ ግንዛቤውም አላደገም፡፡ እንዲህ ባሉ አካባቢዎች ተደራሽ የሆነ ቴክኖሎጂ ማየት ያስደስታል፡፡ ዛሬ የፈጠራ ሥራውን በገጠር ካደረገ እንግዳ ጋር ነው ቆይታ ያደረግነው፡፡

          እንግዳችን ወጣት ፍቃዱ ዳዲ በራተሰን የሴቶች፣ ወጣቶችና ህፃናት ልማት ድርጅት ውስጥ የሚዲያና ቴክኖሎጂ አስተባባሪ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ድርጅታቸው ችግር ፈቺ ፈጠራዎችን ለተጠቃሚው ማድረስ ነው፡፡ ፈጠራዎችን ያበረታታል፤ይፈጥራል፤ፈጠራው ደግሞ ለውጥ የሚያመጣና  ከአንዱ ወደሌላው የሚያሸጋግር መሆን አለበት ብሎ እምነት ይዞ የሚንቀሳቀስ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ በአሁኑ ጊዜም ቴክኖሎጂ ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች እየሰራ ይገኛል፡፡በኦሮሚያ ምሥራቅ ሸዋ አድአ ወረዳ ውስጥ በ27 ቀበሌዎች ውስጥ ስለተሰራው የፈጠራ ሥራ ነው የገለፀልን፡፡

   የፈጠራ ሥራው

    ዲጂታል ቤተ መፅሐፍት /ላይብረሪ/ ወይም ዳታ ኢኮሲስተም ተብሎ ይጠራል፡፡ በትምህርት ቤቶች፣በጤና ተቋማት፣በግብርና ህብረት ሥራ ማህበራት እና በሌሎችም የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ አገልግሎት ይሰጣል፡፡በእነዚህ ተቋማት ውስጥ የሚሰጡ አገልግሎቶች፣እቅዶቻቸውና ተግባራቸውን እንዲሁም የተቋማቱን እቅድ ማወቅ ለሚፈልግም ሆነ የተሰሩና ያልተሰሩ ሥራዎችን ለመከታተል የሚያስችል ፈጠራ ነው፡፡ቴሌ ኮንፈረንስም ለማካሄድ ያግዛል፡፡

  ፈጠራው የተሰራበትና አጠቃቀሙ

    ፈጠራው በመስመር አልባ ወይም ዋየርለስ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣የሚያስፈልገው የስልክ ቀፎ ሲም ካርድና ታብሌት የተባሉ መሣሪያዎች ነው፡፡በዚህ ፈጠራ አገልግሎት ለማግኘት የስልክ ቁጥር አያስፈልግም፡፡በክብ መልክ የተዘጋጀችውን ቁልፍ በጣት መጫን ብቻ ነው፡፡መነጋገሪያውን በጆሮ ላይ አድርገው አንዱን ቁልፍ  ሲነኩት ምን መረጃ እንደሚፈልጉ ይጠየቃሉ፡፡መረጃ ሰጭው ከሚፈልጉት ጋር ያገናኝዎታል፡፡መረጃውን ተቀብሎ ወደሚፈልጉት የሚያስተላልፈው የመረጃ ባለሙያም ማንነትዎን አያውቅም፡፡ስለዚህ ሚስጥርዎ የተጠበቀ ነው፡፡የመረጃ አገልግሎቱ በሚሰጥበት ቦታም ሲደራጅ በነፃነት ሊጠቀሙ በሚችሉበት አካባቢ ሲሆን፤አገልግሎቱም በነፃ የሚሰጥ ነው፡፡

  ፈጠራው የተተገበረበት ቦታ

     ፈጠራው በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በስፋት ተከናውኗል፡፡ በሶስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ በትምህርት ቤቱ አቅራቢያ ነው የተተከለው፡፡ተማሪዎች የትምህርት ቤታቸውን ዕቅድ በጋራ ያቅዳሉ፡፡በጋራ ያቀዱት ሥራ የት እንደደረሰ መከታተል ያስችላቸዋል፡፡በትምህርት ቤታቸው ውስጥ ችግር ሲያጋጥማቸውም ወደሚመለከተው አካል መረጃ በማድረስ መፍትሄ ይፈልጋሉ፡፡ ወቅታዊ መረጃም ከፈለጉ በቀላሉ ማግኘት ይችላሉ፡፡

   ፈጠራው ያስገኘው ጥቅም

    ተማሪዎች መረጃን ከሚፈልጉበት ቦታ ከማግታቸውና መረጃንም ለሚፈለገው አካል ከማድረሳቸው በተጨማሪ በገጠር ትምህርት ቤቶች በአንዳንዶቹ የሚስተዋለውን የተማሪ መጽሐፍት ጥመርታ ችግር ያቃልላል፡፡መረጃውን በመገልበጥ በጆሮ ማዳመጫ  በመጠቀም የመፅሐፍ ችግራቸውን መፍታት ይችላሉ፡፡ፈጠራው ይሄን አገልገሎት ማግኘት የሚያስችላቸው ተደርጎ በመሰራቱ የአማርኛ፣የእንግሊዝኛና የሂሣብ መፅሐፍ ችግሮቻቸውን በዚህ ፈጠራ በመጠቀም ማቃለል ችለዋል፡፡ በተጨማሪም የሴትና የወንድ መፀዳጃ ቤት ተለይቶ ባለመሰራቱ የተፈጠረውን ችግር ለሚመለከተው አካል በማድረስ ችግራቸውን የፈቱ ትምህርት ቤቶችም ይጠቀሳሉ፡፡ 

  የፈጠራ ሥራው ዋና ዓላማና የወደፊት አቅጣጫ

     የፈጠራ ስራው በአንድ አመት አገልግሎቱም ውጤታማ መሆኑን ማረጋገጥ ችሏል፡፡ ትምህርት ቤቶች በዘላቂነት እንዲያስቀጥሉት ግንዛቤ በመፍጠር ድርጅቱ ያግዛል፡፡ ድርጅቱ የፈጠራ ሥራውን ኦሮሚያ ክልል እና የፌዴራል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት እንዲያወቀው አድርጓል፡፡ይህ መሆኑ ፈጠራው ዘለቄታ እንዲኖረው ያግዛል፡፡እስካሁን ባለውም ከመንግሥት ጥሩ ድጋፍ በመደረጉ ፈጠራውን ለማስፋት መልካም አጋጣሚ ነው፡፡

    ራትሰን የሴቶች፣የወጣቶችና የህፃናት ልማት ድርጅት ይህን የፈጠራ ሥራውን በቅርቡ የክርስቲያን በጎ አድራጎት ልማት ማህበራት ህብረት (ሲ አር ዲ ኤ) በተለያየ የልማት ሥራ ማህበረሰብን ተጠቃሚ በማድረግ የላቀ አስዋፅኦ ላበረከቱ የህብረቱ 13 አባል ድርጅቶች እና 3ግለሰቦች የእውቅና ሽልማት በሰጠበት ልዩ ዝግጅት ላይ ኤግዚቢሽን አቅርቦ ሥራውን አስተዋውቋል፡፡  

ለምለም ምንግሥቱ

 

Published in ማህበራዊ

የማያውቁት አገር አይናፍቅም ሲባል እሰማለሁ። እኔ ግን የማላውቃቸው የምስራቅ ኢትዮጵያ ከተሞች ሀረር ከነምንጣፏ፣ድሬደዋ ከነአሮጌው ሰፈሯ፣አሰበ ተፈሪ ከነብርቱካኗ፣ በሰሜኑም ቢሆን ባህር ዳር ከነ ጣናዋ፣ ጎንደር ከነ ፋሲለደሷ፣ ደቡቡም ምእራቡም ሁሉም ....ጭራሽ እንደልጅነት ትዝታ ነው የሚናፍቁኝ።

አሁንም የማያውቁት አገር አይናፍቅም ሲባል እሰማለሁ። እኔ ግን መቼም እንደማላየው እያወቅሁም እንኳ ቀዩ ባህር ይናፍቀኛል። ዛሬም ፊያሜታ ያለች ይመስል የምፅዋ ማእበልና ንፋስ ይናፍቀኛል፤ ዳህላክ ደሴቶቹ፣ አዱሊስ ወደቡ፣ መርከቦቹም ሁሉ ባህሮችን ሲቀዝፉ በምናቤ እያየሁ ይናፍቁኛል፤ የማውቃት አዲስ አበባ ይልቁን እየናፈቀችኝ አይደለም!... እንደተናካሽ የቤት እንስሳ ሲመሽ የሚፈታው ልቤ የዛሬ ቅብጠቱ ይሄ ሆነ፡፡ በናፍቆት ማእበል መመታት፡፡

እየናፈቀችኝ ውቢቷ ባህር ዳር ላይ ከተምኩ ‹‹ ተቀበል እንግዲህ›› አዝማሪው ነው፡፡ ግለቱ ከተፋፋመበት አምሳል ምትኬ የባህል ምሽት ጉሸማ የተሞላበት ቅኔያዊ ግጥሞችን እየኮመኮምን ነው፡፡ ፊት ለፊቴ ከተቀመጡት ጥንዶች በቀር ሁሉም ከመጠጡ በላይ በግጥሞቹ ሰክሯል፡፡ ኮሚኒስታዊ  የሚመስል የማያቋርጥ ጭብጨባ ያስተጋባል፡፡ ሁሉም ለማሲንቆ ሰግዷል፡፡ ለከበሮም አጎብድዷል፡፡ እልም ያለ የጥበብ ዛር፡፡

የቤቱ ጩሀት ከጆሮ በላይ ነው፡፡ እንደውም ከዚህ ቀደም  አንድ ሰው የጎረቤቱን ትንሽ ልጅ ከበራፋቸው ላይ ያገኝና ‹‹ታዲያስ ማሙሽ ትላንት የተወለደው ህጻኑ ወንድምህ እንዴት ነው ?›› ቢለው ማሙሽ መልሶ ‹‹ እሱም ወዲያ ጥለው ቁራ ቢኖረን ይሻል ነበር፡፡ ካለ ጩኸት ስራ የለውም፡፡›› በማለት የመለሰለትን አስታወሰኝ፡፡ ከዘፈኑና ግጥሙ በላይ መልእክት አልባ ጩኸቶች አየሉብኝ፡፡

ዘመኑ የዘፈንና የጫት ምርት የበዛበት ሆኗል፡፡ በእርግጥ በዚህኛው ቤት ድብልቅ የአገር ባህል ዘፈንና ትውን ጥበብ ይታያል፡፡ ዳሩ ግን ባህሉ ዘመናዊነትን ተከናንቧል፡፡ በእኔ አገላለጽ ‹‹እየደረቁ መበስበስ›› ይባላል፡፡ ለምሳሌ ጸሀይ መሀል ዝናብ ሲጥል ዝናቡ ላይ የቆመ ሰው እየደረቀ ይበሰብስ የለ ልክ እንደዛ ማለት ነው፡፡ ወይ ባህላችንን ወይ መጤውን አልተቀበልን እንገርማለን እኮ፡፡ ምርጡን የጎጃም እንቅጥቅጥ ዘመናዊ በሆነው የአደናነስ ስልት ለመንቀሳቀስ ይቃጣናል፡፡

ብቻዬን እዝናናለሁ ብዬ ከገባሁበት ባህል ቤት ብቸኝነት ቁዘማ የመሰለው አዝማሪ ጠጋ ብሎ በግጥም ሊኮረኩመኝ ሲል ጠጋ ብዬ ገንዘብ እንደምሸልመው ስነግረው ወደ ሌሎቹ አቀና፡፡ ለካስ በአዝማሪ ቤትም ኪራይ ሰብሳቢነት ይሰራል፡፡ ወይ ጉድ፡፡ 

በነገራችን ላይ ስለ ኪራይ ሰብሳቢነት ሲነሳ ለመንግስት መስሪያ ቤት አዲስ የሆነ ሰው የመጀመሪያ ስብሰባውን ሲያደርግ በመድረኩ ‹‹ ሁላችንም በኪራይ ሰብሳቢነት መጥፎ ድረጊት ተጠምደናል!›› የሚል አስተያየት ሲሰነዘር ሰምቶ በተራው የመናገር እድል ሲሰጠው ‹‹ በነገራችን ላይ ቅድም የተነሳው የኪራይ ሰብሳቢነት አስተያየት እኔን አይመለከተኝም፤ እኔ ያለችኝ አንዲት ጠባብ ክፍል ቤት ናት ለእኔም አልበቃችኝም እንዴት ብዬ ነው እሷን አከራይቼ ኪራይ የምበላው?›› ሲል ቤቱ በሳቅ አውካካ፡፡

‹‹የቤቴ መቃጠል ለትኋኑ በጀው›› የሚል አገርኛ ምሳሌ አውቃለሁ፡፡ ድብልቅልቅ ያለው የዝላዩና ሁካታ ድባብ አትኩሮቴን ጨመረልኝ፡፡ ከባህል ቤቱ ከመውጣቴ በፊት ብዙ ነገሮችን ለመታዘብ ሞከርኩ ነገር ግን ስሜት ነውና እኔም ለሙከራ ያክል ትከሻዬን ማንቀሳቀስ ጀመርኩ፡፡ ደግነቱ ጨለማ ሆነ እንጂ የእኔን አጨፋፈር ላየ ሰው ለሳምንት የወሬ አጀንዳ ሳልሆን አልቀርም ነበር፡፡ አጠገቤ የነበረው አንድ ሰው በስካር መንፈስ እግሩ ከእጁ ጋር ተሳስሮ እስኪጠፋበት ድረስ መሬት ላይ እየወደቀ እየተነሳ ይጨፍራል፡፡ አዝማሪዎቹ እንደጨረሱ  የጥላሁን ዘፈን ካልተከፈተልኝ ብሎ ቀወጠው ዲጄውም ተሳስቶ ይሁን አውቆ…. በማይታወቅ ምክንያት የነዋይን ዘፈን ከፈተ በስካር የጦዘው ሰውም ዘፈኑ የጥላሁን መስሎታል መሰለኝ… በነዋይ የጥቅምት አበባ ዘፈን… አይ ጥልሽ አይ ጥልሽ… እያለ ይደንስበት ጀመር፡፡ ራሱን እስኪስት ድረስ ጥለሁንንና ነዋይን መለየት አቃተው፡፡

ባህር ዳርን በቀን እንደማየት የሚያስደስተኝ ነገር የለም፡፡ ንጋትን እየናፈቅኩኝ ስገላበጥ አደርኩኝ፡፡ የጸሀይ ብርሀን ካረፍኩበት ክፍል ውስጥ በመስኮት ብቅ አለች፡፡ ፍጥነት በተሞላበት ሁኔታ ልብሴን ለባብሼ ቁርስ ቢጤ ቀምሼ ሞቅ ሲል ወደ ገበያው መሀል አቀናሁ፡፡ 

ቆይታዬን ለሌላው ጊዜ ተወት ላድርግና በዚህ መሀል ያየሁትን አንድ ነገር ብቻ ጣል አድርጌ ልለፍ፡፡ በሄድኩባቸው ገበያዎች ሁሌም ሰዎች ሲከራከሩ ማየት ደስታዬ ነው፡፡ ክርክራቸው እየናረ ሲመጣ በጥሩ ደራሲ የተጻፈ ድራማ ይመስላል፡፡ ቴአትር ቤት ገብቼ ከማየው ተውኔት አይተናነስም፡፡ እናም የገና በአል እየደረሰ በመሆኑ በግ መግዛት አቅሙ ባይኖረኝም ለገዢዎች ዋጋውን ለመናገር የበግ ገበያ ውስጥ ተሰየምኩ፡፡ በገጠር አደግኩኝ ባይ አንድ ሰው ለገና በአል ጓደኛውን በግ ሊያጋዛ ወደ ገበያ ተያይዘው መጡ፡፡  በብዙ በጎች ላይ አቃቂር እያወጣ ሲያማርጥ አየሁት፡፡ ኋላም የአንዱን በግ አፍ አላቆ አየና ይሄስ የሸረፈ ነው! ቢለው በትችቱ ያልተደሰተው በግ ሻጭ ‹‹ ይተውት ጌታው ወርቅ ይተከልለታል ›› ብሎ መለሰለት፡፡

የገበያ አሰሳዬን ጨርሼ በመውጫው አካባቢ ስደርስ ያላሰብኩት ነገር ገጠመኝ፡፡ ከእኔው መኖሪያ መንደር ሸፍታ ወደ ቀድሞ አድባሯ የተመለሰች ጉብል መንደር ዳር ቆማ አገኘኋት፡፡

ልጅት ከዛሬ ሁለት አመት በፊት ባህረ ገብ ከሆነችዋ ውቢቷ የጣና ዳር ፈርጥ ዘጌ በአንድ አዲስ አበቤ የፍቅር ቋንቋ ተወትውታ አብራው ኪሎ ሜትሮችን ተጉዛ ከሰፈሬ ከተመች፡፡  በባዶ እጅ በሙሉ ልብና የዋህነት፡፡ የቀዬዋ ዘዬና ልማድ አለቀቃትም፡፡ በሶፋ መቀመጫ መደብ ያምራታል፣ ለመዋቢያዋ ከቅባት ይልቅ ቅቤ ያሻታል፣ ከኤሌክትሪኩ ምጣድ ይልቅ ኩበት አንድዶ መጋገር ይቀናታል፡፡ ግን ግን ስልጣኔን ያለመረዳት አይደለም ማንነት እዚህ ድረስ ዘልቆባታ እንጂ፡፡ አርባ ሽንሽን ያልተለያት ልጅት አርባ ጊዜ ትሳቀቃለች፡፡ በራሷ ሳይሆን እሷን በሰፈሯት ዘመነኛ መሳይ ዘማዊያን፡፡

የፍቅር ዳርቻው ብዙ ሳይጓዝ ከእለታት በአንዱ ቀን አርባ ሽንሽኗን እንደለበሰች ኢዲስ አበቤው አዲስ ወዳጅ ከስራ ውሎ ሲመጣ ‹‹ ጌታዬ እግርዎን ይለአለኡ! ዘርጉና ልጠቦት›› አለች፡፡ ከመንደሬው ኪስ አጣቢ ሌላ እግር አጠቢ ተገኘ፡፡ ‹‹ለዘመናት ኪሴን እንጂ እግሬን የሚያጸዳልኝ አልነበረም፤ እነሆ የሰከነች አክባሪ ወዳጅ ስጦታ በማግኘቴ ፈጣሪ ይመስገን፡፡›› አለ፡፡ ከማስመሰል ተቆጥቦ ውስጡን ሀሴት ሞልቶት፡፡

ይህንን ያዩ እነ ‹‹እንብላውና እንጋጠው›› ጥጋ ጥግ መሄዱ ቢያስጨንቃቸው ከማታለል ይልቅ ማማለልን ተያያዙት፡፡ ከንፈርን የጦም በየአይነት የተበላበት ትሪ ማስመሰል፣ ህጻን ልጅ ዘሎ የማይደርስበትን ቀሚስ ቢጤ መልበስ፣ ሰባት ሰው ጎትቶ ማውለቅ የማይችል ጥብቅብቅ ያለ ሱሪ መልበስ ወዘተ… የማማለያ ዘዴዎችን በመጠቀም ስርአት አክባሪውን ማስቀናት ስራቸው ሆነ፡፡ ልብን ንቆ ለውስጣዊ ውበት ያደላው አቶዬም አስኮብልሎ ያመጣትን ልጅት ፈትቶ ሌላ አገባ፡፡ በዚህ የተጎዳች ልጅት የት እንደገባች ሳይታወቅ ከረመች፡፡ ፈርጥጣ የገባችበት ባህር ዳር ግን ርቀቱን አቅርቦ ስውሩን አርቅቆ እንዳያት አደረገኝ፡፡  ከገበያው ጫፍ ላይ… ሳምንት ይቀጥላል፡፡

አዲሱ ገረመው

Published in መዝናኛ
Friday, 05 January 2018 22:32

ሳምንቱ በታሪክ

የ‹‹ብርሃንና ሰላም›› ጋዜጣ 93ኛ ዓመት የምስረታ መታሰቢያ

በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃንና የጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ያለው ‹‹ብርሃንና ሰላም›› ጋዜጣ የተመሰረተው (ለሕትመት የበቃው) ከ93 ዓመታት በፊት፣  (ታኅሳሥ 23 ቀን 1917 ዓ.ም) ነበር፡፡

አንጋፋው ‹‹ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት›› መስከረም 3 ቀን 1914 ዓ.ም በንጉሥ ተፈሪ መኮንን (የኋላው ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ) መኖሪያ ግቢ ውስጥ ጨው ቤት በሚባለው ባለ ሁለት ክፍል ቤት ውስጥ ስራውን ጀመረ፡፡ ታኅሣሥ 23 ቀን 1917 ዓ.ም ደግሞ ‹‹ብርሃንና ሰላም›› የተባለውን ጋዜጣ ማተም ሲጀምር ስሙንም ከዚሁ ጋዜጣ ወረሰና ‹‹ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት›› ተባለ፡፡ ይህም ማተሚያ ቤቱ ጋዜጦችን እንዲያትም (የማተም አገልግሎት እንዲሰጥ) አስቻለው፡፡ 

‹‹ብርሃንና ሰላም›› ጋዜጣ  በ500 ቅጂዎች ያህል በሳምንት አንድ ጊዜ (ሐሙስ ዕለት) ይታተምና ይሰራጭ የነበረው በሁለት ፈረሰኞች አማካኝነት እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። ጋዜጣው ሲመሰረት (ከ1917) ጀምሮ እስከ 1921 ዓ.ም ድረስ የጋዜጣው ዲሬክተር (ዋና አዘጋጅ) የነበሩት አቶ ገብረክርስቶስ ተክለሃይማኖት የተባሉት የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ስራ አስኪያጅ ነበሩ፡፡ በ1921 ዓ.ም አቶ ማኅተመወርቅ እሸቴ የጋዜጣው ዲሬክተር (ዋና አዘጋጅ) ሆኑ፡፡   

አልጋ ወራሽ ንጉሥ ተፈሪ መኮንን ጊዜው ለኢትዮጵያ የብርሃንና የደስታ እንዲሆን በመመኘት (በማሰብ) የጋዜጣውን ስያሜ ‹‹ብርሃንና ሰላም›› ብለው እንደሰየሙት ይነገራል!

ብርሃንና ሰላም!      

ተፈስሒ ኢትዮጵያ ሀገረ ገነት፣ እስመ በጽሐ ብርሃንኪ ወራሲ መንግሥት

አንተነህ ቸሬ

Published in መዝናኛ

በምስራቅ ህንድ አካባቢ በ280-550 ምዕተ ዓለም ባሉት ጊዜያት እንደተፈጠረ የሚነገርለት የቼዝ ስፖርት ጨዋታ በብዙዎች ዘንድ ለመወደድ ብዙ ጊዜ እንዳልወሰደበት ይነገራል፡፡ የሙስሊሙ አለም ፐርሽያ ግዛትን ሲቆጣጠር ስፖርቱ መዳረሻውን አስፍቶ በማዕከላዊ እስያ ኡዝቤኪስታንም የወቅቱ ተወዳጅና ተመራጭ ጨዋታ ሆኖ እንደነበር ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ቡክ ኦፎ ቼዝ›› የሚለው መጽሃፍ እንደሚያትተው ደግሞ ወደ ምስራቁ የእስያ አህጉር በተለይም ወደ ቻይናና ደቡብ ምስራቅ እስያ መቼና እንዴት እንደተስፋፋ የተደራጀ መረጃ ባይኖርም ስፖርቱ ከጥንት ጀምሮ ተወዳጅ መሆኑንና ወደ ምዕራብ አውሮፓና ሩሲያ በ9ኛው ክፍለ ዘመን መስፋፋቱን  ያስቀምጣል፡፡ በመካከለኛው ክፍለ ዘመን ቼዝ ከባህል ትውፊቶች አንዱ ተደርጎ ተወስዶ የጦርነት ስትራቴጂ ማስተማሪያና ራስን የማብቂያ መሳሪያ በመሆንም አገልግሏል፡፡ 

  ቼዝ ከሁሉም የሰሌዳ (ቦርድ) ላይ ስፖርታዊ ጨዋታዎች መካከል ቀዳሚው ሲሆን፤ በአለም አቀፍ በተለይም በቤተ-መንግስት ደረጃ፣ በወታደራዊ መስክ በተሰማሩ ሰዎችና በምሁራን ዘንድ ተወዳጅና ተመራጭነቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ጨዋታው ነገሮችን በፍጥነት የመረዳት፣ በትኩረት የማሰብ (critical thinking)፣ ቀጣይ ሊሆን የሚችለውን የመተንበይና ፈጣን የሂሳብ እውቀት የሚጠይቅ ሲሆን፤ በርካታ ፖለቲከኞችና የአገር መሪዎች ከሚያዘወትሯቸው የቦርድ ላይ ጨዋታዎች መካከልም ተጠቃሽ ነው፡፡

  የቼዝ ስፖርት ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ዘመናት ቢቆጠሩም እስካሁን ድረስ በብዙዎች ዘንድ የአስተሳሰብ ክፍተት መኖርና ስለ ስፖርቱ ጠቀሜታ በተገቢው ሁኔታ ባለመረዳት እድገቱ የእድሜውን ያህል አልፈጠነም፡፡ በተለይም የስፖርቱ መጫወቻ ቁሳቁሶች ዋጋ ውድ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በሁሉም አካባቢ ስፖርቱ እንዳይዘወተርና እንዳይታወቅ ምክንያት ሆኗል፡፡

  የቼዝ ስፖርት ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ዓመታት ቢያስቆጥርም ከእድሜ ጠገብነቱ አኳያ የስፖርቱ ጥቅም እስካሁን ተገቢውን እውቅና አግኝቶ ሁሉም ዜጋ ሊጫወተው የሚችል ስፖርት ሆኖ አይገኝም፡፡ በአብዛኛው የጨዋታው መጫወቻ ቦርድና ቁሳቁሶቹ ዋጋቸው ከፍተኛ መሆን ደግሞ ሁሉም በቀላሉ በነፍስ ወከፍ እንዳያገኘውና ጨዋታውን እንዳይችለው ምክንያት መሆኑ ይጠቀሳል፡፡

   የዘርፉ ሰዎች እንደሚናገሩት አንድ የቼዝ መጫዋቻ ቦርድ ከ500 ብር በላይ ዋጋው ከፍ ማለቱ ስፖርቱ በሁሉም የመጀመሪያ፣ ሁለተኛና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለማስፋፋት ተግዳሮት ከመፍጠሩ ባሻገር ዜጎች የስፖርቱን ጠቀሜታ በተገቢው ሁኔታ በመረዳት ከስፖርቱ ጋር እንዳይተዋወቁ አድርጓል፡፡ በመሆኑም የቼዝ ስፖርት አስፈላጊ ግብዓቶችን በአካባቢና በቀላል ዋጋ ከሚገኙ ነገሮች በማሟላት ስፖርቱ ለዜጎች የሚያስገኘውን ጠቀሜታ ማጎልበት እንደሚያስፈልግም ይናገራሉ፡፡ በዚህ ረገድ በየካ ክፍለ ከተማ በተለምዶ 41 እየሱስ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር አካባቢ የሚገኘው ትግል ለነጻነት የመጀመሪያ ደረጃ አፀደ ህጻናት ትምህርት ቤት የቼዝ ስፖርትን ለማጎልበትና ለማስፋፋት በአካባቢው ከሚገኙ ግብዓቶች በመጠቀም የስፖርቱ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ማሟላትና ተማሪዎች በቀላሉ ስፖርቱን እንዲለማመዱ ማድረግ ችሏል፡፡

  ከአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ እንዲሁም ከክፍለ ከተማው የስፖርት ስልጠና ተሳትፎና ውድድር ስራ ዘርፍ የተውጣጡ የስራ ሃላፊዎች ሰሞኑን በትምህርት ቤቱ በመገኘት የልምድ ልውውጥ ያደረጉ ሲሆን፤ በወቅቱ እንደተገለጸው ትምህርት ቤቱ ለስፖርቱ በተገቢው ሁኔታ ማደግ አንዱ ተግዳሮት የሆነውን የቁሳቁስ ችግር ከማቃለል ጀምሮ መጫወቻ ቁሳቁሶችን ከጭቃና ሻማ በመስራት እንዲሁም አስፈላጊውን ቀለም በመቀባትና አስመስሎ በቀላሉ በማዘጋጀት ስፖርቱ በትምህርት ቤቱ እንዲስፋፋ ትልቅ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ በየካ ክፍለ ከተማ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች በቼዝ ስፖርት ቀዳሚ ከመሆኑ ባሻገር በተምሳሌትነት የሚጠቀሱ የከተማዋ ቼዝ ተወዳዳሪዎች የሚፈልቁበትም ነው፡፡

  በትምህርት ቤቱ የሂሳብ መምህር የሆነው ዳንኤል ቱፋ ተማሪዎች በሂሳብ ትምህርት የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ፣ የማሰብ፣ በቀላሉ የመረዳትና የመተንበይ ክህሎታቸው እንዲያድግ የቼዝ ስፖርት በትምህርት ቤቱ እንዲስፋፋ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ሲሆን፤ ለስፖርቱ አስፈላጊ ቁሳቁሶች ከጭቃና ከሻማ እንዲሰሩ በማድረግ በጥቂት ወጪ በርካታ ተማሪዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የበኩሉን አስተዋጾ ማድረጉንም ይገልጻል፡፡

   መምህር ዳንኤል እንደሚለው፤ ልጆቹ የቼዝ ስፖርት ጨዋታን እየተጫወቱ በሄዱ ቁጥር ውስብስብ ችግሮችን የመረዳት ክህሎታቸው እያደገ ስለሚሄድ የአዕምሯቸው ትምህርት የመቀበል አቅም እየሰፋ ይሄዳል፡፡ በተግባርም ወደ ጨዋታው የገቡ ልጆች በሂሳብና በሌሎች ማህበራዊ ሳይንስ ትምህርቶች ላይ ልዩነት እያመጡና እየተሻሻሉ ነው፡፡

  ትምህርት ቤቱን ከዘጠኝ አመት በፊት ሲቀላቀል ምንም አይነት የቼዝ ስፖርት እንዳልተጀመረና በተለያዩ መጽሃፍና ድረ-ገጾች ለሂሳብና ለሌሎች ሳይንስ ትምህርቶች   የሚኖረውን ጠቀሜታ በመረዳት በትምህርት ቤቱ ለማስጀመር የትምህርት ቤቱ አስተዳደር አንድ የቼዝ ቦርድ እንዲገዛ መጠየቁን የሚናገረው መምህር ዳንኤል፤ በመምህራን የተጀመረው ቼዝ ስፖርት በተማሪዎች መታወቅ መቻሉ የበርካቶችን ልብ መያዙንና በየዕለቱ የተጫዋቾች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ይናገራል፡፡ የተማሪዎችን ፍላጎት ማሳካት የሚችል ብዛት ያለው ቦርድና አስፈላጊ ቁሳቁሶች ለማሟላት በጭቃና በሻማ መስራት መጀመራቸውንም ያስረዳል፡፡

  ‹‹በአሁኑ ወቅት በትምህርት ቤቱ 40 የቼዝ ስፖርት መጫወቻ ቦርዶች ያሉ ሲሆን፤ 70 የሚሆኑ ተማሪዎች ስፖርቱን በትክክል በማወቅ በትርፍ ጊዜያቸው ልምምድ እያደረጉ ነው፡፡ ስፖርቱ ብዙ ስሌት እንድትሰራ የሚያስገድድ በመሆኑ ተማሪዎች ብዙ እንዲያስቡና አዕምሯቸውን እንዲያሰሩት ያደርጋል፡፡ ይህም ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች ስፖርቱ ከተጀመረ በኋላ በተለይ የሂሳብ ትምህርት ውጤታቸው መሻሻል አሳይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የቼዝ መጫወቻ ቦርድ በ500 ብር የሚገኝ ቢሆንም ጥሩ የተባለው ግን እስከ አንድ ሺ ብር ይደርሳል፡፡ ትምህርት ቤቱ በአሁኑ ወቅት የጎደሉትን ላሟላ ቢል አርባ ሺ ብር ወጪ ያደርግ ነበር›› በማለትም መምህር ዳንኤል ያብራራል፡፡

   የተማሪዎችን የትምህርት ጊዜ ላለመሻማት ብዙ ጊዜ እንዲጠቀሙ የሚፈቀደው ምሳና ሻይ ሰዓት ላይ ብቻ መሆኑንና ይህም በውድድር መንገድ እንደሚካሄድ ገልጸው፤ የተለያዩ እንቆቅልሾችን እንዲፈቱና ደቂቃ በመያዝ በፍጥነት ለመጨረስ ልምምድ የሚያደርጉባቸው ፕሮግራሞች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ትምህርት ቤቱ ለከተማዋ የቼዝ ስፖርት ውድድር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ሲሆን፤ ባለፈው አመት በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል በተደረገው የቼዝ ስፖርት ውድድር በወንዶች ለክፍለ ከተማው ዋንጫ አምጥቷል፤ በሴቶች ሶስተኛ ደረጃ ሲወጣ፤ በፕሮጀክት በተደረገ ውድድር ክፍለ ከተማውን ወክለው ሁለተኛ መውጣት ችለዋልም ብለዋል፡፡

   መምህር ዳንኤል ስፖርቱን ለማሳደግ ትምህርት ቤቱ ጥረት ቢያደርግም የክፍለ ከተማው አመራር ተገቢ ትኩረት ባለመስጠቱ፤ አንዳንድ የስፖርቱ ግንዛቤ የሌላቸው ወላጆችም ጨዋታው ቁማር መስሎ ስለሚታያቸው ልጆቻቸውን እንዳይለምዱት የሚከለክሉበት አጋጣሚ መኖሩና በትምህርት ቤቱ የሚገኙ የስፖርቱ ተሳታፊዎች በፕሮጀክት አለመታቀፋቸው በውጤታማነት ላይ ተግዳሮት መፍጠሩን አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም የክፍለ ከተማው ትምህርት ጽህፈት ቤት ተገቢውን ትኩረት መስጠት ቢችል ስፖርቱን በተሻለ ሁኔታ ማሳደግ የሚቻልበት ምቹ ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል፡፡

   በትግል ለነጻነት የመጀመሪያ ደረጃ አፀደ ህጻናት ትምህርት ቤት የ6ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ሰለሞን መብሬ የቼዝ ጨዋታ ከፍተኛ ጥቅም እያስገኘለት መሆኑንና በትምህርቱም የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግብ እንዳገዘው ይናገራል፡፡

  ተማሪ ሰለሞን እንደሚገልጸው፤ ቼዝ ጨዋታ አንድ ሰው በማህበራዊ ህይወቱ ፈጣን እንዲሆን ችግሮችን በቀላሉ የመፍታት ክህሎት እንዲያሳድግና ከሰዎች ጋር ያለው ማህበራዊ ትስስር ጠንካራ እንዲሆን ከማድረጉ ባሻገር በኢኮኖሚያዊ መስኮችም ስኬታማ እንዲሆን ይረዳል፡፡ ‹‹በተማሪዎች መካከል የሚደረገው የቼዝ ስፖርት ውድድር በስፖርቱ ብቻ ሳይሆን በትምህርቱም እርስ በርሳችን እንድንፎካከርና ለበለጠ ውጤት እንድንሰራ አነሳስቶናል›› ይላል፡፡

የቼዝ ጨዋታ ሴቶች በማህበራዊ ህይወታቸው ላይ ያላቸውን ከፍተኛ ሚና እንዲሁም የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ መረዳት ያስችላል፡፡ ሴት የለችም ማለት እርሷ የምትሸፍናቸውና የምትወጣቸው ሃላፊነቶች እንደሚጓደሉና በስተመጨረሻም ለውድቀት እንደሚዳርጉ በጥልቅ ለመገንዘብም ይረዳል የሚለው ተማሪ ሰለሞን፤ በአጠቃላይ የአስተሳሰብ ክህሎትን ለማሳደግ ይረዳል ባይ ነው፡፡  

  በአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ስልጠና ተሳትፎና ውድድር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በኃይሉ በቀለ ቼዝ በዓለም ደረጃ የኦሎምፒክ ጨዋታና ውጤቱ በጣም ከፍተኛ ሲሆን፤ የሚጫወቱት በእውቀት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚደርሱ ሰዎች ናቸው፡፡ ሆኖም ስፖርቱ በሚጠበቀው ደረጃ በከተማዋ አላደገም፡፡ ለዚህም አንዱ ምክንያት የግብዓት እጥረት ሲሆን፤ ትግል ለነጻነት የመጀመሪያ ደረጃ አፀደ ህጻናት ትምህርት ቤት በቀላሉ የስፖርቱ ግብዓቶችን በማሟላት ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች ተሳታፊ እንዲሆኑ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

   በትምህርት ቤቱ የተሻለ ተሞክሮ ያለበት በመሆኑ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋትና ሌሎች የሚማሩበትን አጋጣሚ ለመፍጠር ከትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር ፕሮግራሞች እንደሚዘጋጁና በከተማ ደረጃ እውቅና የሚያገኝበት መድረክ እንደሚኖር አቶ በኃይሉ አስረድተዋል፡፡ በትምህርት ቤቱ በስፖርቱ የሚሳተፉ ተማሪዎች በፕሮጀክት አለመያዛቸው በልጆቹ ላይ ውስንነት ፈጥሯል፡፡ ይህን ለማስተካከልና ልጆቹ በፕሮጀክት በመታቀፍ ወደ ተሻለ ደረጃ የሚደርሱበትን መንገድ ለመዘርጋት ስፖርት ቢሮው ስራዎችን እየሠራ መሆኑንና ከጥር 1ቀን 2010ዓ.ም ጀምሮ ልጆቹ በፕሮጀክት ታቅፈው የሚሰሩበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ በተጨማሪም ቼዝ የአዕምሮ ስፖርት እንደመሆኑ በፖሊሲ ደረጃ እንዲታቀፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንና በአፍሪካ ሰባት አገራት ተመርጠው ተሞክሯቸው እየተጠና ነው በማለትም አቶ በኃይሉ አረጋግጠዋል፡፡

   አቶ በኃይሉ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ስፖርቱ በሚጠበቀው ደረጃ እንዳያድግ የግብዓት ችግር አንዱ ምክንያት ቢሆንም አስተሳሰቡ ካለ በቀላሉ ከጭቃና ከሻማ በመስራት መጠቀም ይቻላል፡፡ ትግል በነጻነት ትምህርት ቤት በጭቃና በሻማ በመስራት መጠቀም እንደቻለ ሌሎችም ከተመሳሳይ ቁሳቁሶች፣ በፕላስቲክ፣ በወረቀት እንዲሁም ከቀንድ በመስራት ስፖርቱን ማስፋትም ይችላሉ ነው ያሉት፡፡

 ዑመር እንድሪስ

Published in ስፖርት

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት በአገሪቱ የፀጥታ ጉዳይ ዙሪያ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት እየመከረ ይገኛል፡፡

ረፋድ ላይ የተጀመረውን የምክክር መድረክ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈጌሳ እየመሩት ይገኛሉ፡፡

በመድረኩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የፌደራልና የክልል የፀጥታ አካላት፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ታድመዋል፡፡ ውይይቱን በተመለከተ የመከላከያ ሚኒስትሩ ከሰዓት መግለጫ እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡

መግለጫው እንደተሰጠ ዝርዝሩን እናቀርባለን።

በብሩክ በርሄ

ፎቶ በሀዱሽ አብርሃ 

Published in የሀገር ውስጥ

ሰሞኑን በኢራን ከተሞች በመካሄድ ላይ ያሉት የተቃውሞ ሰልፎች ምክንያታቸው ለረጅም ዓመታት ሲብላሉ የቆዩ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እንደሆኑ የፖለቲካ ተንታኞች እየገለፁ ይገኛሉ፡፡ ለብዙ ዓመታት ስር ሰድደው የቆዩ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ከኑሮ ውድነት መናር ጋር ተደምረው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢራናውያን አገሪቱን ከ30 ዓመታት በላይ የመራውን መንግሥት ለመቃወም አደባባይ እንዲወጡ እንዳደረጋቸው ይነገራል፡፡

የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት በአብዛኛው በነዳጅ ላይ የተንጠለጠለ እንደሆነና አገሪቱን በተከታታይ ያስተዳደሩት መንግሥታትም በዚያች አገር ከብዙ ዓመታት በፊት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ተንሰራፍተው የሚስተዋሉትን መዋቅራዊ ችግሮች ማስተካከል እንዳልቻሉ የኢራንን ጉዳዮች በቅርበት የሚከታተሉ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልፃሉ፡፡

ከችግሮቹ መካከልም የውጭ ኢንቨስትመንት እጥረትና የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ቅጥ ያጣ ጣልቃ ገብነትና አድራጊ ፈጣሪነት ዋነኛ ተጠቃሽ እንደሆኑ ይገለፃል፡፡ የአገሪቱ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 9.6 በመቶ፣ የስራ አጥነቱ ደግሞ 13 በመቶ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይሁን እንጂ ሌሎች መረጃዎች እንደሚሉት ደግሞ ዋጋ ግሽበቱና የሥራ አጥነቱ ቁጥር ከላይ ከተጠቀሱት እጥፍ ይሆናል፡፡

እ.አ.አ ታኅሣሥ 28 ቀን 2017 በሀገሪቱ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛውን ስፍራ በያዘችው ማሻድ ከተማ በመንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ላይ ተቃውሞ የሚያሰሙ ሰልፈኞች ለተቃውሞ አደባባይ ወጡ፡፡ ተቃውሞው አድማሱን እያሰፋ ሲሄድ ግን የሚሰሙት ድምፆችም ይዘታቸውን እቀየሩ መጡ፤ በመንግሥት ላይ እንዲሁም በሀገሪቱ መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ሆሚኒ ላይ ፖለቲካዊ ተቃውሞዎች መስተጋባት ጀመሩ፡፡

ከተቃውሞ ሰልፈኞቹ መካከል ብዙዎቹ ወጣቶች እንደሆኑ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ እስካሁን በቁጥጥር ስር ከዋሉት የተቃውሞ ሰልፈኞች መካከልም ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወጣቶች እንደሆኑ ተነግሯል፡፡  በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ያለው ተቃውሞ ለሕይወት መጥፋትና ለንብረት መውደም ምክንያት እንደሆነም ተገልጿል፡፡ እስካሁን ድረስም ከ20 በላይ ሰዎች እንደሞቱና ከ500 በላይ የሚሆኑት ደግሞ እንደታሰሩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች በፕሬዚዳንት ሐሰን ሮሃኒ አስተዳደር የተነደፉ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ለተቃውሞው መነሻ እንደሆኑ ሲገልፁ፣ ሌሎች ደግሞ ሕዝቡ በሀገሪቱ መንግሥትና በመንፈሳዊ መሪው ክፉኛ እንደተማረረ ያብራራሉ፡፡ መጂድ ነመሃመድ የተባሉ ኢራናዊ ጸሐፊ በበኩላቸው ሙስና፣ ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ እና ጥብቅ ሃይማኖታዊ አስተዳደር ለተቃውሞው መነሻ ምክንያቶች እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡  

በርካታ ኢራናውያን አገራቸው እ.አ.አ በ2015 ከዓለማችን ኃያላን አገራት ጋር ያደረገችው የኑክሌር ድርድር በአገሪቱ ላይ የተጣሉት ማዕቀቦች ተነስተው የኢኮኖሚ መነቃቃት በመፍጠር በአገሪቱ የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት ያረጋጋዋል የሚል ተስፋ ሰንቀው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ድርድሩ የታሰበውን ለውጥ ሊያመጣ አልቻለም፡፡

የአረብ ፖለቲካ ተንታኝና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ማህጁብ ዝዌሪ፣ ‹‹የኢራን ሕዝብ ከኑክሌር ድርድሩ መልካም ውጤት ይገኛል ብሎ ተስፋ አድርጎ የነበረው ስሌት የተሳሳተ ነበር፤ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን ከያዙ በኋላ ሕዝቡ የፕሬዚዳንቱን ፖሊሲዎች ከግምት ውስጥ አላስገባቸውም፤ ሲጀመርም ድርድሩ ለኢራን ጠቃሚ አልነበረም›› ብለዋል፡፡

የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ስምምነቱን ሊሰርዘው እንደሚችል በተደጋጋሚ መግለፁ የውጭ ባንኮች በአገሪቱ ለሚከናወኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ገንዘብ ለማቅረብ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ 

ዶናልድ ትራምፕ በፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት አበክረው ሲናገሯቸው ከነበሩት ጉዳዮች መካከል አንዱ አገራቸው አሜሪካን ጨምሮ ኃያላኑ ከኢራን ጋር የተፈራረሙትን የኑክሌር ስምምነት እንደሚሽሩት ደጋግመው ማሳወቃቸው ነበር፡፡ ሰውየው እ.አ.አ በ2016 ፕሬዚዳንታዊ ስልጣኑን ከያዙ በኋላም ስምምነቱ አደጋ ውስጥ ገባ፡፡ ባለፈው ጥቅምት ወር የአገሪቱን የኑክሌር መርሃ ግብር በተመለከተ የቀረበላቸውን ስምምነት አልፈርምም ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ይባስ ብለውም አንድ ዓመት ሊሞላው ቀናት በቀሩት የፕሬዚዳንትነት ስልጣን ጊዜያቸው እስካሁን ድረስ በኢራን ላይ ኢኮኖሚዋን የሚያሽመደምዱ ሁለት ማዕቀቦችን ጥለዋል፡፡ 

መቀመጫውን ዋሽንግተን ዲ.ሲ ያደረገው የኢራናውያን-አሜሪካውያን ብሔራዊ ካውንስል መስራችና ፕሬዚዳንት የሆኑት ትሪታ ፓርሲ በበኩላቸው ኢራን በተለያዩ ጊዜያት የተጣሉባት ማዕቀቦች በሀገሪቱ ተንሰራፍቶ ከሚስተዋለው ሙስና ጋር ተደምሮ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ክፉኛ እንደጎዱት ይገልጻሉ፡፡

‹‹በተለያዩ ጊዜያት በኢራን ላይ የተጣሉት ማዕቀቦች የአገሪቱን ኢኮኖሚ በእጅጉ አሽመድምደውታል፤ የኑክሌር ስምምነቱን እንደሚሽረው በሚዝተው የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር ምክንያት ስምምነቱ የኢኮኖሚ ቀውሱን ከማረጋጋትና ከማሻሻል ይልቅ አባብሶታል›› ይላሉ፡፡

ይሁን እንጂ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የኑክሌር ስምምነቱን አደጋ ላይ መጣሉ ለተቃውሞው መነሳት ብቸኛው መንስዔ ተደርጎ ሊቆጠር አይችልም ተብሏል፡፡ በሀገሪቱ ያለው ስራ አጥነት፣ የዋጋ ንረትና የውጭ ኢንቨስትመንት እጥረት ለተቃውሞው ተጨማሪ ምክንያቶች ተደርገው ተጠቅሰዋል፡፡ ሀገሪቱ በምትከተላቸው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ምክንያት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይ ደግሞ በምጣኔ ሀብታቸው ከፈረጠሙት ከአሜሪካና ከአውሮፓ ሀገራት ለመገለል ተገድዳለች፡፡

ፕሮፌሰር ማህጁብ ዝዌሪ እንደሚሉት፣ በዚያች አገር ከብዙ ዓመታት በፊት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ተንሰራፍተው የሚስተዋሉትና ሀገሪቱን ባስተዳደሩት መንግሥታት ሊቀረፉ ያልቻሉት መዋቅራዊ ችግሮች በተለይ የሕግ አውጭውንና የፋይናንሱን ዘርፍ ቀፍድደው ስለያዙት አገሪቱ ለዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስርዓት ዝግ እንድትሆንና የከባድ ሙስና መነኻሪያ ለመሆን ተገድዳለች፡፡                     

እስላማዊው አስተዳደር ስልጣን ከያዘ ወዲህ መዋቅራዊ ችግሮቹ ስር መስደዳቸውንና መንግሥትም በየጊዜው ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ ሲገጥመው በዜጎች ላይ ታክስ እየጨመረ የምጣኔ ሀብት ቀውሱን እንዳባባሰው ይናገራሉ፡፡ ባለፈው ወር የአገሪቱ ፓርላማ በነዳጅ ላይ ሊደረግ የታሰበው የዋጋ ጭማሪ ላይ ውይይት መካሄዱ ይታወሳል፡፡

ኢራን በአካባቢው ፖለቲካ ውስጥ ያላት ተሳትፎም ለተቃውሞው መነሻ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በእርስ በእርስ ጦርነት በምትታመሰው በሶሪያ ፖለቲካ ውስጥ እጇን እንዳስገባች የምትታማው እስላማዊቷ ሪፐብሊክ፣ የፕሬዚዳንት በሺር አል-አሳድ አጋር እንደሆነች ይነገርላታል፡፡ ተቃውሞ ሰልፈኞቹም የኢራን መንግሥት በሺር አል-አሳድን ለመርዳት የሚያወጣው ገንዘብ አላስፈላጊ የሆነ ወጪ እንደሆነ ድምፃቸውን አስተጋብተዋል፡፡

የአረቢያ ፋውንዴሽን ምክትል ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ፊራስ ማቅሳድ፣ የአገሪቱ ዜጎች «ኢራን ከኑክሌር ስምምነቱ በኋላ ያገኘችው ገንዘብ የዋለው በኢራቅ፣ በሶሪያ እና በሊባኖስ ለሚገኙ ታጣቂዎች ነው» ብለው እንደሚያስቡ ገልፀዋል፡፡ ሰልፈኞቹ የአገሪቱ መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ሆሚኒ ከስልጣናቸው እንዲወርዱ መጠየቃቸው ከተቃውሞው ጀርባ ስር የሰደዱ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች እንዳሉ ያመለክታሉ ብለዋል፡፡ 

‹‹በቀውስ የተናጠ ኢኮኖሚ ባለበት ሁኔታ ታክስ በመጨመር የሕዝብን ገንዘብ ለመዝረፍ የሚደረግ እንቅስቃሴ የሕዝብን ቁጣ ከመቀስቀስ ያለፈ ፋይዳ የለውም›› ብለዋል፡፡

የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የሚባለው ቡድን ቅጥ ያጣ ጣልቃ ገብነትና አድራጊ ፈጣሪነት ለፕሬዚዳንት ሃሰን ሮሃኒ መሰናክል እንደሆነባቸው ይናገራል፡፡ ለዘብተኛ አቋም አላቸው የሚባሉት ፕሬዚዳንቱ ልዩ ልዩ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ለመወሰን ሲሞክሩ ከዚህ ቡድን የሚገጥማቸው ፈተና እጅግ ከባድ ነው ይባላል፡፡ በዚህም ምክንያት ፕሬዚዳንቱ ለውጥ የማምጣት እድላቸው የጠበበ ይሆናል፡፡   

በቴህራን ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት መሀመድ ማራንዲ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ለበርካታ ዓመታት በዚህ ቡድን ሀገራዊ ኢንቨስትመንት ላይ የተንጠለጠሉ እንደሆኑና አገሪቱ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተጣሉባት ማዕቀቦች ምክንያት  መንግሥት ዋና ዋና ፕሮጀክቶቹን ለዚሁ ቡድን እንዲያለማ ስለመስጠቱ ይናገራሉ፡፡

የአረብ ፖለቲካ ተንታኝና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ማህጁብ ዝዌሪ እንደሚሉት ደግሞ፣ ኢራን የውጭ ኢንቨስተሮችን እንዳታገኝ መሰናክል የሆነው የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ቡድኑ ነው፡፡ ቡድኑ ሀገሪቱ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያስችሏትን ሕጎች እንዳታፀድቅ በፓርላማው ላይ ጫና እንደሚያሳድር በመጠቆም፡፡ ለአብነት ያህል ባለፈው ዓመት ፕሬዚዳንት ሮሃኒ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ያደረጉት ሙከራ ‹‹የምዕራባውያንን ባህል የሚያበረታታና ከእስላማዊ መርሆች ጋር ተፃራሪ›› ተብሎ በወግ አጥባቂ ፖለቲከኞች እንደተጨናገፈባቸው ያስታውሳሉ፡፡

የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ቡድኑ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ገደብ የለሽ ጣልቃ ገብነትና የብቻ ተጠቃሚነት  ለተቃውሞው አንድ ምክንያት ሊጠቀስ እንደሚችልም ያምናሉ፡፡

የኢራናውያን-አሜሪካውያን ብሔራዊ ካውንስል መስራችና ፕሬዚዳንት የሆኑት ትሪታ ፓርሲ በበኩላቸው፣ ‹‹አብዛኛው ኢራናውያን የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የሚባለው ቡድን ከሕግ በላይ የሆነ የሕገ-ወጦች ስብስብ እንዲሁም በአገሪቱ ለተንሰራፋው ሙስና ዋነኛው ተጠያቂ እንደሆነ ያምናሉ›› ብለዋል፡፡

አሁን አገሪቱን በመምራት ላይ ያለው የኢራን እስላማዊ መንግሥት እ.አ.አ በ1979 ስልጣን ከጨበጠ ወዲህ  በውስጣዊና በውጫዊ ጉዳዮች (ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች) ላይ ሀይማኖት ተኮር አካሄድ መምረጡ ይገለፃል፡፡ ይህም የኢራን መንግሥት ለሽብርተኞች ይፋዊ ድጋፍ ያደርጋል በሚል ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር እንዳቃቃረው ይነገራል፡፡   

       አንተነህ ቸሬ

 

Published in ዓለም አቀፍ

ከአንድ ሳምንት በፊት የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም «በመረጃ ነፃነት አዋጅ 590/2000» ዙሪያ ያካሄደውን የዳሰሳ ጥናቱ በአዋጁ አተገባበር ዙሪያ ያሉ ተግዳሮቶችን ምንነት ላይ በአገር ውስጥ ከሚገኙ የሚዲያ ተቋማት ጋር ለግማሽ ቀን የቆየ ውይይት አድርጎ ነበር። በውይይቱ ላይ ከመንግስት እና ከግል የመገናኛ በዙሀን የተወከሉት ተሳታፊዎች በአዋጁ ተግባራዊነት ላይ እያጋጠማቸው የሚገኘውን ተሞክሮ ለማካፈል ሙከራ  አድርገዋል።

መገናኛ አካባቢ በሚገኘው «ቤልቪው ሆቴል» በተደረገው ውይይት ከተነሱት በርከት ያሉ ጉዳዮች ውስጥ ጎልቶ መውጣት የቻለው የመረጃ ነፃነት አዋጁ አተገባበር ላይ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በዳሰሳ ጥናት አማካኝነት በተገኙ ውጤቶች ለማመላከት የተሞከረበት ሀሳብ ነው። ዳሰሳዊ ጥናቱን ያቀረቡት የተቋሙ ሲኒየር ኤክስፐርት አቶ ታደሰ ገዙ ነበሩ። ከዋና ዋና ነጥቦቹ መካከል የቆየና ስር የሰደደ የሚስጥራዊነት ልማድ፣ የፋይል አያያዝና አደረጃጀት ዘመናዊ አለመሆን ፣ የክህሎት እጥረት፣ የህዝብ ግንኙነት የመዋቅር ችግርና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶቹ የመረጃ ነፃነት አዋጁ ተግባራዊ እንዳይሆን እንቅፋት ከሆኑት መካከል እንደሚገኙበት በጥናቱ ተመላክተዋል። እነዚህን ሀሳቦች በዝርዝር ምን አይነት ትርጉም እንዳላቸው ባለሙያው  ያቀረቡትን ዳሰሳዊ ጥናት መሰረት አድርገን የምንመለከተው ይሆናል።

በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የመገናኛ ብዙሀን ያነሷቸው ነጥቦች ከላይ ከቀረበው ዳሰሳዊ ጥናት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ይዘት ቢኖራቸውም በራሳቸው የሚቆሙ እና አዳዲስ ምልከታዎችን እና ተግዳሮቶችን የሚያስቀምጡ ነበሩ። እነዚህ የመገናኛ በዙሀን ባለሙያዎች  በአዋጅ ላይ ከፍተኛ የግንዛቤ እጥረት እንዳለ እና ዋንኛውና የመጀመሪያው ችግር እርሱ መሆኑን ለማስቀመጥ ሞክረዋል። በተለይ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎች ከበላይ ማኔጅመንቱ በሚደርስባቸው ጫናም የተጋነኑ እና ትክክል ያልሆኑ መረጃዎችን ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን በተለይም ለመንግስት መገናኛ በዙሀን መስጠታቸው ተቀባይነት እና ተአማኒነታቸውን ጥርጣሬ ውስጥ እየከተተባቸው እንደሆነ አበክረው ገልፀዋል። ይህ የመረጃ ነፃነት አዋጁን የሚፃረር መሆኑንም ነው ለመግለፅ ። ከዚህም ሌላ የመገናኛ ብዙሀንን እኩል ያለመመልከት እና ለአንደኛው ወገን አድልቶ መረጃ የመስጠት ሁኔታም በስፋት እንደሚስተዋል አስረድተዋል።

የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በህገ መንግሥታችን አንቀፅ 55(15) መሠረት፣ በአዋጅ ቁጥር 211/1992 የተቋቋመ እና በተጨማሪም የአዋጅ 590/2000 ክፍል ሦስት (የመረጃ ነፃነት ሕግን) የማስተግበር ሥልጣን የተሰጠው ህገ መንግስታዊ ተቋም ነው። ከላይ ያነሳነውን የውይይት አጀንዳም ከመገናኛ ብዙሀን እና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር የውይይት መድረኮችን በመፍጠር አዋጁ ተግባራዊ እንዲሆን በመስራት ላይ መሆኑንም እየገለፀ ይገኛል። መገናኛ ብዙሀኑ ብሎም ሌሎች በጉዳዩ ላይ በቅርበት የሚመለከታቸው አካላት ተቀራርበው በባለቤትነት መንፈስ መስራት መቻላቸው አዋጁ እየገጠመው ያለውን የተፈፃሚነት ችግር ለማስወገድ እንደሚረዳ ነው ዳሰሳዊ ጥናቱን በባለሙያዎቹ አማካኝነት ያሰራው የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የሚገልፀው። በተለይም መገናኛ በዙሀኑ የመረጃ ነፃነት አዋጁን መርሆች ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረጉ እና ግንዛቤ በማስጨበጡ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸውም ተገልጿል።

የተቋሙ ሲኒየር ኤክስፐርት አቶ ታደሰ ገዙ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ስልጣን እና ተግባርን አስመልክቶ ሲናገሩ፤ በአዋጅ ቁጥር 211/1992 መሠረት በተለያዩ ጥፋቶች ምክንያት አስተዳደራዊ በደሎች እንዳይፈፀሙ የአስፈፃሚውን አካል የመቆጣጠር እና መልካም የመንግሥት አስተዳደር እንዲሰፍን የመስራት፤ በአዋጅ 590/2000 ክፍል ሦስት መሠረት የመረጃ ነፃነት ሕግን የማስተግበር ሥራ የመስራት ብሎም ሦስቱም የመንግሥት አካላት የመረጃ ነፃነት ሕግን እንዲተገብሩና እንዲያከብሩ ለማድረግ እንደሚሰራ ይገልፃሉ። በዚህም መሰረት የመረጃ ነፃነት መብትን የሚደነግገውን አዋጅ በህብረተሰቡ እና በተለያዩ ተቋማቶች ውስጥ በማስተዋወቅ ክትትል በማድረግ በትክክለኛው መንገድ ተግባራዊ እንዲሆን የተለያዩ ጥረቶች እየተደረገ መሆኑንም ያነሳሉ። ሆኖም ግን በሂደቱ ላይ በርከት ያሉ ፈተናዎች እያጋጠሙ መሆኑን ነው የሚናገሩት።

«አዋጁ የመረጃ ነፃነት ህግን ከተቀበሉ አለም አቀፍ ተቋማትና አገራት ምርጥ ተሞክሮ የወሰደ ነው» በማለት የሚያስረዱት አቶ ታደሰ፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአንቀፅ 37 የአዋጁ ማስፈፀሚያ ደንቦችን ማውጣት፣ የአዋጁን ማስፈፀሚያ ደንቦች አፈፃፀም የመከታተልና ተገቢ እገዛዎችን የማድረግ፣ እንደ መንግስት ተቋም አዋጁን ከማስተግበር በተጨማሪ  የመረጃ ነፃነት አዋጅን ተግባራዊነት የሚቆጣጠራቸውን ተቋማት በቅርበት የመከታተል፣ ሌሎች ተቋማት ለምክር ቤቱ ሪፖርት ሲያቀርቡ የመረጃ ነፃነት ሪፖርት ማካተታቸውን መቆጣጠር እንዲችል ስልጣን እና ሀላፊነት ተሰጥቶታል በማለት ይናገራሉ።

በተመሳሳይ ፍርድ ቤቶች እንደ ማንኛውም የመንግስት ተቋም አዋጁን ተግባራዊ ማድረግ፣ ከሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ቀጥሎ በመረጃ ጉዳዮች ላይ የሚቀርቡላቸው አቤቱታዎችን እንዲሁም ይግባኞችን መርምረው ፈጣን ውሳኔ የመስጠት ሀላፊነት አላቸው። እንደ ባለሙያው ገለፃ ይህ ተግባር እና ሀላፊነት  በአዋጁ ላይ በአንቀፅ አንቀፅ 34 ላይ ሰፍሮ ይገኛል። የሚዲያ አካላት ሚና በተመለከተው በዚህ አዋጅ ላይ በዝርዝር የሰፈሩ ድንጋጌዎች አሉ። በዚህም በአብዛኞቹ አገሮች ሚዲያ ሀሳቦችን በማመንጨትም ሆነ በማሰራጨት የጎላ ድርሻ ስላለው ሰብዓዊ መብትን በማሳወቅና በማጎልበት መጠቀም አስፈላጊ ነው። ለዚህም ተቋማት ከሚዲያ ጋር እንዴት እንደሚሰሩ ስትራቴጂዎችን መንደፍና የሚሰሩባቸውን አርዕስተ ጉዳዮች መለየት አስፈላጊ ነው። በመሆኑም በባለድርሻ አካላት መካከል ውይይቶች እንዲካሄዱ ማድረግ፣ የመረጃ ነፃነት ሕጉ ተግባራዊነት ለልማት፣ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበት፣ ሙስናን ለመከላከል ብሎም ለዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ለማዋል እንዲጠቀሙበት እድሉን የሰጣል። በተለይም አዋጁ ያለውን ጠቀሜታ ግንዛቤ ማስጨበጥ፤ መልካም ተሞክሮዎች እንዲስፋፉ የሌሎች ሀገሮችንም ሆነ በሀገራችን ያሉትን ማበረታታትና ማስፋፋት ላይ ሊሰሩ እንደሚገባ ያመላክታል።

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው አዋጁ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት በዝርዝር በመረጃ ነፃነት ዙሪያ ተግባራዊ ስራዎችን እንዲያከናውኑ እድል መክፈት ቢችልም እንደ አቶ ታደሰ ገለፃ፤ ህጉ ወደ መሬት እንዲወርድ ለማድረግ ከፍተኛ የቅንጅት እና ትስስር ጉድለት ይታያል። በዋናነት ይህን ዳሰሳዊ ጥናት ለማድረግ የተፈለገበት ምክንያትም በአዋጁ አተገባበር ላይ ያሉትን ክፍተቶችና ተግዳሮቶች ለይቶ መፍትሄዎቻቸውን  ለማስቀመጥ ነው።

ተግዳሮቶች በርካታ እና የየራሳቸው ባህሪ ያላቸው መሆኑንም የዳሰሳ ጥናቱን ያቀረቡት ባለሙያ ይናገራሉ። ከላይ በመግቢያችን ላይ እንዳስቀመጥነው እነዚህ ማነቆዎቹ በጥንቃቄ ሊታዩ የሚገቡ እንደሆነ የሚያመላክቱ ጉዳዮችን መገንዘብ እንችላለን። አቶ ታደሰ በጥናቱ ላይ በቀዳሚነት የሰፈረው ችግር፤ የመረጃ ነፃነቱ አዋጅ ተግባራዊ እንዳይሆን ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች ተርታ የሚሰለፈው «የቆየና ሥር የሰደደ የምሥጢራዊነት ልማድ» መሆኑን ያነሳሉ። ይህ ማህበረሰባዊ እና ተቋማዊ ልማድ ማንኛውም ሰው መረጃ የማግኘት እና ለፈለገው አላማ ለማዋል የሚያደርገውን ጥረት የሚገድብ ነው። ስለዚህ ይህን ልማድ በቀዳሚነት መቀየርና ሁሉም ሰው ከፈለገው ተቋም እና ህጋዊ አካል ተገቢ የሆነ መረጃን እንዲያገኝ ማመቻቸት አስፈላጊ ይሆናል።

አንድን መረጃ በፍጥነትና በተፈለገው መጠን ለማግኘት እድሉ ሊመቻች እንደሚገባ በአዋጁ ላይ ሰፍሯል። ሆኖም ይህ ህግ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ በተቀላጠፈ ሁኔታ ሲተገበር አይስተዋልም። ለዚህ ችግር እንደ ሁለተኛ ተግዳሮት «የፋይል አያያዝና አደረጃጀት ዘመናዊ አለመሆን» ነው በማለት የዳሰሳ ጥናት አቅራቢው ይናገራሉ። ደካማ የመረጃ አያያዝ ስርአቱ መሻሻል ካልቻለ በፍጥነት እና በሚፈለገው መጠን መረጃውን ለጠየቀው ሰው ለመስጠት እንደሚያዳግትም ያስረዳሉ። ይህን ችግር ለማስወገድ ሁሉም ተቋማት በቅንጅት መስራታቸው አስፈላጊ መሆኑንም አበክረው ይገልፃሉ።

የመረጃ ነፃነት አዋጁ «ማንኛውም ሰው» መረጃ ከፈለገበት ተቋም የማግኘት መብቱን ይደነግጋል። ሆኖም ይህ ህግ አንዳንድ ውስን ክልከላዎችን ያስቀምጣል። ማለትም የተፈለገ መረጃ በአገር እና በዜጎች ደህንነት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ተመዝኖ አሉታዊ ጎኑ ከጎላ ክልከላ እንዲደረግበት ይፈቅዳል። ነገር ግን ይህችን ውስን ድንጋጌ መነሻ በማድረግ ጉዳት የማያስከትሉ መረጃዎችን ጭምር የመከልከል አንድምታ ይታያል። ጥናት አቅራቢው ይህ ጉዳይ በሁለት መልክ ይከሰታል ይላሉ «መረጃ ሰጪውም መረጃ ተቀባዩም  የተሳሳተ ግንዛቤ  በመያዛቸው እና የክህሎት እጥረት በተለይ በመረጃ ሰጪ በኩል» በመኖሩ። ይህም የመረጃ ነፃነቱ ከወጣ ጀምሮ ተግባራዊነቱን ከሚፈታተኑት ተግዳሮቶች ውስጥ እንደሚመደብ መገንዘብ አስፈላጊ ይሆናል።

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርነው በውይይቱ ላይ የተነሱ በርካታ ተግዳሮቶች ለመረጃ ነፃነት አዋጁ በተገቢው መንገድ አለመተግበር በወሳኝ ነጥብ የተዘረዘሩ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም  «የሕግ ማዕቀፎች አለመሟላት»    ህጉ አዝጋሚ ለውጥ እንዲኖረው በር መክፈቱን ዳሰሳዊ ጥናቱ ያመለክታል። «በመንግሥት አካላት ዘንድ የቁርጠኝነት ችግር» መኖሩን ጠቁሞም እነዚህ አካላት ህግ ከማውጣት በዘለለ የሚያጋጥሙ ቁልፍ ችግሮችን ለይቶ መፍትሄ በመስጠት ተግባራዊ እንዲሆን አለመስራታቸውን ያሳስባል። የመንግስት ተቋማት በአዋጁ አንቀጽ 36/3 መሠረት ተጠሪ ለሆኑበት ምክር ቤት ሪፖርት አለማቅረባቸው ሌላኛው የችግሩ መንስኤም መሆኑን ለማመላከት ይሞክራል። ምክር ቤቶችም ተገቢውን ክትትል አለማድረጋቸው ፣ በጀትና የሰው ኃይል እጥረት መኖሩ በራሱ ቀላል ግምት ሊሰጠው የማይገባ መሆኑን ያነሳል። የችግሩ መነሻ ለሆኑ ተግዳሮቶች እንደየ ባህሪያቸው መፍትሄ ማፈላለጉና ቅንጅታዊ አሰራር መፍጠሩ እንደመፍትሄ ሊወሰድ የሚገባው ጉዳይ መሆኑን  በማስቀመጥ ያጠቃልላል።

ዳግም ከበደ

Published in ፖለቲካ

ለምግብነት ከሚውሉ አትክልቶች አንዱ የሆነው ጎደሬ በገበያ ላይ ቢቀርብም የድንች፣ካሮትና ሌሎች አትክልቶችን ያህል ተጠቃሚ የለውም፡፡ ዝርያው ለየት ያለ በመሆኑ ብዙዎች የሚበላ አይመስላቸውም፡፡ ጎደሬ በደቡብ ክልል በተለይም በዳውሮ፣ በከምባታ፣ በሀዲያ፣ ወላይታና ጅማ አካባቢዎች የሚዘወተር የምግብ አይነት እንደሆነና ልማቱም በአካባቢዎቹ በስፋት እንደሚከናወን ከአካባቢው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ጎደሬ በተተከለ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ የሚደርስ ሲሆን፣ ከአንድ ሄክታር እስከ ሰባት መቶ ኩንታል ምርት ይሰበሰባል፡፡ከአራት አመታት በፊት የነበሩ መረጃዎች እንደሚያመ ለክቱት በክልሉ 35ሺህ 688ሄክታር መሬት በጎደሬ ምርት የተሸፈነ ሲሆን፣ በወቅቱ 24 ሚሊዮን981ሺ 600ኩንታል ተገኝቷል፡፡ ከዚህ ውስጥም 8ሚሊዮን 266ሺ607ኩንታል ምርት የተገኘው ከወላይታ ዞን ነው፡፡ ጎደሬ 16ያህል ዝርያዎች ሲኖሩት በስፋት እየለማ የሚገኘው ግን በአረካ ግብርና ምርምር ተቋም ተሻሽሎ የወጣው «ወሎሶዋን» የተባለው ዝርያ ነው፡፡

ጎደሬ የምርቱ የቆይታ ጊዜ ከሁለት ወር የበለጠ አይደለም፡፡ ተቀቅሎ ለምግብነት እንዲውል ከማድረግ ውጭ ሌላ አማራጭ ባለመኖሩ የምርት ብክነቱ ከፍተኛ እንደሆነም ይነገራል፡፡በአሁኑ ጊዜ ግን ጎደሬን በማቀነባበር ብክነቱን የመቀነስ ሥራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ቆራርጦ በማድረቅ ከጤፍ፣ከበቆሎና ከሌሎችም የህል ዘሮች ጋር አብሮ በማስፈጨት እንጀራ ዳቦ ገንፎ ተዘጋጅቶ ለምግብነት እየዋለ ነው፡፡ጥቅሙም በብዙዎች እየታወቀ ተፈላጊነቱ ጨምሯል፡፡ የማቀነባበሩ ሥራ የአካባቢውን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥም አይነተኛ መላ እንደሆነ እየተነገረለት ነው፡፡

በወላይታ ዞን ዳሞሶሬ ወረዳ አንጮጮ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ የሆኑት አቶ ተፈራ ሌንጫ እንደነገሩን ጎደሬ ተቀነባበሮ ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት እርሳቸውም ሆኑ የአካባቢው አርሶ አደር ገበያ ላይ የሚያውለው በጣም በርካሽ ዋጋ ነው፡፡ በኩንታል ከፍተኛው ዋጋ ከ50እስከ80ብር ነበር፡፡ ጎደሬ ውሃማ ስለሆነ ቶሎ ይበላሻል፡፡በመሆኑም በተገኘው ዋጋ በመሸጥና የተቻለውን ያህል ለምግብነት በማዋል ለመጠቀም ጥረት ያደርጋሉ፡፡ አቶ ተፈራ ከእርሻ መሬታቸው ግማሹን ሄክታር በማልማት በዚህ መልኩ በመጠቀም ነው ያሳለፉት፡፡ካለፉት አራት አመታት ወዲህ ግን ጎደሬን ቀቅሎ መብላት ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ የእህል ዘሮች ጋር በመደባለቅ በፈለጉት መልክ ጋግረው ለምግብነት ማዋል መጀመራቸውን ያስረዳሉ፡፡ ተፈላጊነቱም በመጨመሩ የአንድ ኩንታል ጎደሬ ዋጋ እስከ 300ብር ድረስ መሸጥ መጀመሩን ይናገራሉ፡፡

አቶ ተፈራ እንዳሉት ሴንድ ኤ ካው ኢትዮጵያ የተባለ ድርጅት በ2006ዓ.ም መስከረም ወር ላይ በአካባቢያቸው ተገኝቶ ጎደሬ አምራች ለሆኑ አርሶ አደሮች ጥሪ በማቅረብ ጎደሬን በማቀነባበር ጥቅሙን ማሳደግ እንደሚቻል ያወያያቸዋል፡፡ በወቅቱም ለማመን ተቸግረው ነበር፡፡ድርጅቱ ከውይይቱ በኋላም ስልጠና አዘጋጀቶ እንዲሳተፉ በድጋሚ ጥሪ አቀረበላቸው፡፡ እርሳቸውን ጨምሮ የድርጅቱን ጥሪ ተቀብለው  ስልጠና ለመሳተፍ ከተመዘገቡት 125 የአካባቢው ጎደሬ አምራቾች 75ቱ ብቻ ነበሩ የሰለጠኑት፡፡ እርሳቸውም ቢሆኑ ብዙም እምነት አልነበራቸውም፡፡ ስልጠናውን የወሰዱ አርሶ አደሮች ተደራጅተው ጎደሬን በማቀነባበር ተጠቃሚ እንዲሆኑም ድርጅቱ አስፈላጊውን ድጋፍ አድርጎ አደራጃቸው፡፡ አቶ ተፈራም 61 አባላት ያሉት የአንጮጮ ቀበሌ ነዋሪ የጎደሬ ምርት ማቀነባበሪያ ግብይት ህብረት ሥራ ማህበር ሰብሳቢ ሆነው ተመረጡ፡፡ ማህበራቸውን እያገለገሉ በተቀነባበረ ጎደሬ ተጠቃሚ በመሆን ትርፋማ ሆነዋል፡፡

አቶ ተፈራ እንዳስረዱት ማህበራቸው የህብረት ሥራ ማህበር በሚፈቅደው ህግ መሠረት ህጋዊ እውቅና አግኝተው ጎደሬን በማቀነባበር በዱቄት መልክ በማዘጋጀት በመሸጥ ላይ ይገኛሉ፡፡ ምርታቸውን ለትምህርት ተቋማት፣ ለማረሚያ ቤቶችና ለተለያዩ ተቋማት በስፋት ለማቅረብም በማስተዋወቅ ላይ ናቸው፡፡ማህበሩን ለማጠናከርም አባላት በየወሩ እያንዳንዳቸው 10ብር ይቆጥባሉ፡፡ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ አባላቱ በአንድ በኩል የቁጠባ ባህላቸውን እያሳደጉ፣በሌላ በኩል ደግሞ ማህበራቸው ትርፋማ ሲሆን የትርፍ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ጎደሬን የማቀነባበር ክህሎት ማግኘታቸውም ሌላው ጥቅም እንደሆነ ትልቅ እምነት አላቸው፡፡ ማህበሩ ሴንድ ኤ ካው ኢትዮጵያ ባደረገለት የገንዘብ ድጋፍ አንድ ወፍጮ ቤት አቋቁመዋል፡፡ ከዞኑ ባገኘው አምስት ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይም የምርት ማከማቻ መጋዘን ሰርቷል፡፡ማህበሩ በአሁኑ ጊዜ ንብረቱን ጨምሮ ሁለት  ሚሊዮን የሚገመት ንብረት አለው፡፡ ማህበራቸው ጥረቱን በማጠናከር የበለጠ ለማደግ እየተጋ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የማህበሩ አባል ወይዘሮ አበበች መንደዶ ጎደሬ በዱቄት መልክ ተዘጋጀቶ ጥቅም ላይ እንደሚውል ቀድመው አውቀው ቢሆን ብዙ ይጠቀሙ እንደነበር በቁጭት ይናገራሉ፡፡ 10ልጆቻቸውን ጨምሮ 12ቤተሰቦቻቸው ከጎደሬ ውህድ የሚዘጋጀውን ምግብ እንደወደ ዱትና በገበያ ላይ ያለው ተፈላጊነትም ከፍተኛ እንደሆነ ከእስከዛሬው ተሞክሮአቸው ያስረዳሉ፡፡ ማህበሩ ገና በማደግ ላይ እንደሆነ የሚናገሩት ወይዘሮ አበበች በትንሹም ቢሆን ዘንድሮ የትርፍ ክፍፍል ማግኘታቸውን ገልፀውልናል፡፡ ወደፊት ከፍተኛ እንደሚሆን ተስፋ አድርገዋል፡፡

የሴንድ ኤ ካው ኢትዮጵያ የወላይታ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ካሣ እንደገለፁት በአሁኑ ጊዜ በአካባቢው ጎደሬ በማቀነባበር ሥራ ላይ የተሰማሩ አራት ማህበራት ሲሆኑ፣እያንዳንዱ ማህበር ከ45 እስከ 50አባላት አሉት፡፡ ማህበራቱ ጎደሬ ያመርታሉ፤ ያቀነባብራሉ፤ ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ አካባቢው በስራስር ተክሎችና በተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎች እንደሚታወቅም አቶ ተስፋዬ ገልፀዋል፡፡ወደፊት ማህበራቱ በአንድ በኩል ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉትን እንደጎደሬ በተለያየ መልክ በማዘጋጀት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ጥረት እንደሚያደርጉ አመልክተዋል፡፡

የሴንድ ኤ ካው ኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽንና ማርኬቲንግ ሥራ አስኪያጅ አቶ ወድወሰን ተሾመ ድርጅቱ ወደ አርሶ አደሩ መንደር ሲሄድ«ምን አለህ? እንጂ ምን ላድርግልህ ብሎ አይጠይቅም» በማለት እያደረገ ስላለው ድጋፍ እንዳስረዱት አርሶ አደሩ ባለው ሀብት ላይ እሴት ጨምሮ ተጠቃሚነቱን እንዲያሳድግ በገንዘብ በሙያ ክፍሎት እና በተለያዩ ድጋፎች በማገዝ ወደ ሥራ እንዲገቡ ያደርጋል፡፡ ወደሥራ ከገቡ በኋላም የጀመሩትን ሥራ መምራት እስኪችሉ ድጋፍና ክትትል ያደርግላቸዋል፡፡ በዚሁ መሰረት ነው በደቡብ ክልል ጎደሬን በማቀነባበር ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ የተቻለው፡፡

ድርጅቱ ወደ ሥራው ከመግባቱ በፊት ጎደሬ በውስጡ ስለያዛቸው ንጥረ ነገሮች በሀገር ውስጥና በእንግሊዝ በሚገኙ የትምህርት ተቋማት ውስጥ አስጠንቷል፡፡በጥናት ግኝቱም የጎደሬ የፕሮቲን መጠን 6ነጥብ62 በመቶ፣የፋት ወይም የቅባት መጠን 1ነጥብ 63በመቶ፣ ፋይበር 2ነጥብ29 በመቶ፣ አሽ 4 ነጥብ 04 በመቶ፣ ስታርች 77 ነጥብ 75 በመቶ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ለሰውነት ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን መያዙ በተደረገው ጥናት ከተረጋገጠ በኃላ ወደ ሥራ ቢገባም፡፡ የጥናቱ ሥራ ቀጥሏል፡፡ በምን ያህል መጠን ከጤፍ፣ከበቆሎና ከሌሎችም የእህል አይነቶች ጋር ቢቀላቀል ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆን በማስጠናት ጥቅሙን የማሳደግ ሥራ ይሰራል፡፡

አቶ ወንድወሰን እንዳስረዱት ጎደሬን በማቀነባበር ወደ ዱቄት የመለወጡ ተግባር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣የምግብ ይዘት አማራጭን ለማስፋት፣ የገቢ ማስገኛን ለማሳደግ ከማገዙ በተጨማሪ አዲስ የቴክኖሎጂ እውቀት ለማግኘትም ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በማህበር ተደራጅተው መንቀሳቀሳቸው ባጋራ መስራትንና መማማርን ያሳድጉበታል፡፡ የአካባቢ ጥበቃን ለማጠናከርም ይረዳቸዋል፡፡ ድርጅቱ እንዲህ የአርሶ አደሩን ኑሮ ለመቀየር ላበረከተው አስተዋፅኦ የመልካም ተሞክሮ የእውቅና ሽልማት አግኝቶበታል፡፡ ባለፈው  ሳምንት የክርስቲያን በጎ አድራጎት ልማት ማህበራት ህብረት (ሲ አር ዲ ኤ) በተለያየ የልማት ሥራ ማህበረሰብን ተጠቃሚ በማድረግ የላቀ አስዋፅኦ ላበረከቱ የህብረቱ 13 አባል ድርጅቶች እና 3ግለሰቦች የእውቅና ሽልማት ከሰጣቸው መካከል ሴንድ ኤ ካው ኢትዮጵያ ድርጅት አንዱ ነበር፡፡ ከሲ አር ዲ ኤ ለሰራው ሥራ ሽልማት ሲያገኝ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ «ሽልማቱ ለበለጠ ሥራ የሚያነሳሳ ቢሆንም የአርሶ አደሩን ኑሮ ለመቀየርና ሀገሪቷ ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት መደገፍ ትልቅ የመንፈስ እርካታ የሚገኝበት ነው»ሲሉ አቶ ወንድወሰን የድርጅታቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡

ለምለም መንግሥቱ

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 3

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።