Items filtered by date: Saturday, 06 January 2018
Saturday, 06 January 2018 20:08

ሚዲያው ሲቃኝ

ዜና ትንታኔ

ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሁነኛ ድርሻ ካላቸው ተቋማት መካከል የሀገራችን ሚዲያና ፕሬስ በሚገባው ደረጃ ነፃነታቸው ተጠብቆ የህዝብ ዓይንና ጆሮ ሆነው እንዲያገለግሉ የተደረገው እንቅስቃሴ የሚፈለገውን ያህል ውጤት ያላመጣና ዕድገቱም ዘገምተኛ መሆኑ ተገልጿል። ለምን የሚጠበቅበትን ያህል ለውጥ አላመጣም?


የኢህአዲግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ እንዳስቀመጠው በሀገሪቱ ያሉ በክልልም ይሁን በፌዴራል ያሉ የህዝብ የሚዲያ አውታሮች በልማትና በሀገራዊ አንድነት ዙሪያ መሥራት ሲጠበቅባቸው ህዝብን ከህዝብ በሚያራርቅ አፍራሽ ተግባር ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። በመሆኑም በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ ከሕጋዊ አሠራርና ከሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በተፃራሪ የሁከትና የግርግር መልዕክት በህዝብ ሚዲያ የሚተላለፍበትን ዕድል ለመዝጋት የሚያስችሉ እርምጃዎችን እንደሚወስድ አስታውቋል። በዚህ ዙሪያ ምሁራኖችን አነጋግረናል።


አቶ በረከት ሀሰን በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ በቅርቡ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተከስተው የነበሩት ችግሮች እንዲባባሱ አንዳንድ ሚዲያዎች ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ይሄ ሊሆን የቻለው፤ ከህገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ጀምሮ ሚዲያን ለማስተዳደር የወጡ አዋጆችና ህጎች በአግባቡ መተግበር ባለመቻላቸው ነው፡፡ አስፈፃሚውም ኃላፊነቱን መወጣት ባለመቻሉ መሆኑን ይናገራሉ።


መንግሥትም የችግሩን አሳሳቢነት እስከተገነዘበ ድረስ የሚመለከተውን አካል በሙሉ ተጠያቂ ማድረግ ይጠበቅበታል የሚሉት ባለሙያው፤ በዚህ ሂደት አስፈላጊ ከሆነም ያሉትን ህጎች መፈተሽ ይገባል።ተጠያቂነቱም በሥነ ምግባር ብቻ ሳይሆን በወንጀልም እስከ ማስጠየቅ የሚደርስ መሆን አለበት ብለዋል።


የሚወሰደው እርምጃ ለግጭቶች መቀስቀስም ሆነ መባባስ ዋናውን ሚና እየተጫወተ ያለውን ማህበራዊ ሚዲያ ተደማጭነት እንዳይጨምር ይህንን ያካተተ መሆን አለበት። ይህም ከፍተኛ ወጪ ሊጠይቅና ቅሬታዎችም ከተለያዩ አካላት ሊቀርቡ እንደሚችል በመጠቆም፤ ይሄ ካልሆነ ማህበረሰቡ አማራጭ የመረጃ ምንጭ በመፈለግ ወደ ማህበራዊ ሚዲያው ጠቅሎ መግባቱ አይቀሬ ይሆናል ብለዋል።
እንደአቶ በረከት ገለፃ፤ የሚወሰዱ እርምጃዎች በአገሪቱና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ የሚዲያውንና የጋዜጠኛውን ሀሳብን በነጻነት የመግለፅ መብት የማይቃረኑ፣ ተጽእኖ በማይፈጥር መልኩ ማከናወን ይገባል። ምሳሌ በመጥቀስ የተናገሩትም ጀርመን ጥላቻን የሚያስተላልፉ ማህበራዊ ሚዲያዎችን ለመቆጣጠር እስከ ወንጀል ቅጣት የሚያደርስ ህግ ማውጣቷን ነው።


መምህሩ እንደሚሉት፤ የሚዲያ ተቋማት በውስጣቸው ላሉ ጋዜጠኞች ነጻነታቸውን በማይጋፋ ሁኔታ የሥነ ምግባር መመሪያ ማዘጋጀት አለባቸው። የመንግሥት ተቋማትም ለሁሉም ሚዲያዎች መረጃን ያለአድልዎ መስጠት ይገባቸዋል። በአሁኑ ወቅት በግልጽ የሚታየው መረጃን እየመረጡ የመስጠት አካሄድ ህዝቡ ጆሮውን ለሌሎች እንዲሰጥ እያደረገው ይገኛል።


«ሚዲያ አገር የመገንባትም የማፍረስም አቅም እንዳለው ይታወቃል፡፡ በአገሪቱ የሚገኙ ሚዲያዎችም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሚያስተላልፏቸው አንዳንድ መልዕክቶች አፍራሽ ናቸው» የሚሉት ደግሞ በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ከበደ ናቸው፡፡ አቶ ዮሐንስ ይህንንም ሲያብራሩ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የሚገኙ በርካታ ሚዲያዎች የሀገሪቱን ህግ በሚጣረስ መልኩ ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ። ጥሩ ሲሠሩ የነበሩ ሚዲያዎችም እየተበረዙ ናቸው። ይሄ ሊሆን የቻለው ደግሞ መንግሥት በወቅቱ ተገቢ እርምጃ ባለመውስዱ ነው።


መንግሥት እስካሁን ባለው ተሞክሮ ችግር የመለየት ክፍተት የለበትም ነገርግን በወቅቱ እርምጃ ሲወስድ አይታይም። አሁንም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ችግሩ አሳሳቢና ሀገራዊ እንደመሆኑ ግለሰቦችንም ተጠያቂ በሚያደርግ መልኩ ህጎችን መከለስና ለህዝቡ ማሳወቅ ይገባል፡፡ ይሄንን ተገንዝቦ የሚያጠፋ ካለ ደግሞ እርምጃ መውሰድና ለሌሎች ትምህርት በሚሰጥ መልኩ ለህዝብ ይፋ ማድረግ ተገቢ ነው። እስካሁን እንደሚታየው አንዳንድ እርምጃዎች የተወሰዱ ቢሆንም፤ ለህዝብ ይፋ ባለመደረጋቸው ጥፋቶች እንዲደጋገሙ የራሳቸው አስተዋፅኦ አበርክተዋል።


እንደአገር ደህንነት ሲታሰብ ማህበራዊ ሚዲያው አንድ የሚዲያው አካል መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። በእነዚህ ሚዲያዎች የዩኒቨርሲቲ መምህራንን ጨምሮ በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ የተቀመጡ ግለሰቦች ተመሳሳይ ጥፋት ሲፈጽሙ ይታያሉ። አንዳንድ ብዙ ተከታይ ያላቸው ጦማሪዎች ከሚዲያው በላቀ ህዝብን ከህዝብ የሚያቃቅር ሥራ ሲሠሩ ይስተዋላል። ሆኖም ግን መንግሥት እርምጃ ሲወስድ አይታይም። እንደዚህ አይነት እርምጃዎች ያደጉት አገሮችም የሀገራቸውንና የህዝብን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያደርጉት ነው። ይሄ ማለት በሚዲያዎች ላይ አላስፈላጊ ቁጥጥር ይካሄድ ማለት ሳይሆን እያንዳንዱ የሚዲያ ተቋምም ሆነ ባለሙያ ኃላፊነት በተሞላ መልኩ የሚወጣበት ሥርዓት መዘርጋት መቻል ነው።


በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር የሆኑት አቶ ሻለሙ ስዩም በበኩላቸው ማንኛውም ነገር መመራት ያለበት በህግ ነው፤ ሚዲያዎች ደግም መረጃዎችን ሲያስተላልፉ ህግ ማክበር ብቻ ሳይሆን የህዝብን ሰብዕና በማይነካ መልኩ ሊሆን ይገባል ይላሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከናወነ ያለው በተቃራኒው መሆኑን ያምናሉ። አንዳንዶቹ ሚዲያዎች የሚያቀርቧቸው ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ ቀውስ የሚፈጥሩ ዘገባዎች ናቸው። በመሆኑም ቁጥጥር ማድረጉ የሚያጠያይቅ አይሆንም፡፡ ነገርግን የሚወሰደው እርምጃ ህዝቡን ባለቤት ወደሌላቸውና ኃላፊነት ወደ ጎደላቸው የማህበራዊ ሚዲያዎች የማይገፋና በአንጻሩ በሀገር ውስጥ ያሉ ሚዲያዎችን ህግና ሥርዓትን ጠብቀው እንዲሠሩ የሚያስችል መሆን አለበት ብለዋል።


ጋዜጠኞችም ለመገናኛ ብዙኃን የወጡ ህጎች፣ መመሪያዎችና ደንቦች ጠንቅቀው ማወቅና መተግበር ብሎም ሥነ ምግባር በተላበሰና ሀገራዊ ስሜትን በሚጠብቅ መልኩ እንዲሠሩ የሚያስችል መሆን ይጠበቅባቸዋል። በህግ የተከለከሉትን እንዲለዩና የዘገባ ነጻነትም እስከምን ድረስ እንደሆነ እንዲገነዘቡ ማድረግም ይገባል። የሚዲያ ተቋማቱም በስመ ነጻ ሚዲያ ወደ ጥፋት እንዳይገቡ ያለባቸውን ኃላፊነትና የሚጠበቅባቸውን ማሳወቅ አለበት ብለዋል።
አቶ ሻለሙ ጨምረው እንዳብራሩት በአሁኑ ወቅት በተጨባጭ ማህበረሰቡ እውነትም ይሁን ሐሰት በርካታ መረጃዎችን አገኛለሁ ብሎ ጆሮውን ለማህበራዊ ሚዲያ ሰጥቷል።። ለእዚህ የዳረገው በሀገሪቱ ያሉት ሚዲያዎች የህዝቡን ሀሳብ በማስተናገድ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን በሚፈለገው ደረጃና ፍጥነት ተደራሽ ማድረግ ባለመቻላቸውና ፍላጎቱን ባለማርካታቸው ነው። በዚህም ህዝቡ ከሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ያላገኛቸውን መረጃዎች ለማግኘት ወደ ማህበራዊ ሚዲያ አዘንብሏል።


በተጨባጭ ያሉት አሉታዊ ጎኖች እንዳሉ ሆነው፤ ከየትኛውም የሀገር ውስጥ ሚዲያ በተሻለ መልኩ ሀሳብ ሲገለፅ፣ ክርክርና ውይይት ሲካሄድ የሚታየው በእነዚሁ ማህበራዊ ሚዲያዎች ነው። በሌላ በኩል እነዚህ ሚዲያዎች ለሚያቀርቧቸው ዘገባዎችም ሆነ መረጃዎች እውነታነት ምንም ማረጋገጫ የለም። ችግር የሚፈጥሩ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ ሆነው እንኳ ቢገኙ ተጠያቂ የሚሆን የለም። በመሆኑም እርምጃው እነዚህን እውነታዎች መነሻ አድርጎ ማህበራዊ ሚዲያውንም ካላካተተ በሀገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችን የበለጠ ከማባባስ አይዘልም ይላሉ።


በቀጣይ ሚዲያዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር የማህበራዊ ሚዲያዎችን አካቶ ካልወጣ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ችግሮቹ በዚሁ ከቀጠሉ የመባባስ ሁኔታዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያመላክታሉ አቶ በረከት።
መንግሥት ሚዲያውን በሚመለከት ከዚህ ቀደም የወጡ ህጎችንና መመሪያዎችን በትክክል ማስተግበር፣ መሻሻል የሚገባቸው ካሉም እንዲሻሻሉ የማድረግ ኃላፊነት አለበት። ነገር ግን ሚዲያዎች ያለተጠያቂነት መሥራት ከቀጠሉ ችግሮች ተባብሰው የሀገር አንድነትንና ሰላምን የሚያናጋ ችግር እንዲፈጠር በር መከፈቱ አይቀርም ሲሉ አቶ ዮሐንስ ስጋታቸውን ይጠቅሳሉ።


ራስወርቅ ሙሉጌታ

Published in የሀገር ውስጥ

የአገሪቷ የሰላም ሁኔታ ከዕለት ወደ ዕለት እየተስተካከለና እየተሻሻለ መምጣቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት አስታወቀ።

ምክር ቤት በአገሪቱ የፀጥታ ጉዳይ ዙሪያ ባለፈው አንድ ወር ሲያከናውን የቆያቸውን ተግባራት ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ሲገመግም ውሏል፡፡

 የግምገማውን ውጤት በተመለከተ ማምሻስን ለመገናኛ ብዙሐን መግለጫ የሰጡት የመከላከያ ሚኒስትር ሲራጅ ፈጌሳ፤ ዕቅዱ በወጣበት ወቅት የነበረውን አጠቃላይ የፀጥታ ሁኔታና አሁን የተፈፀሙ ስራዎች የተሻለ አፈፃፀም የታየበት መሆኑ እንደተገመገመ ገልጸዋል፡፡

በአንድ ወር ውስጥ በተሰሩ ስራዎች ከዚህ ቀደም የነበረው የሰላም ሁኔታ ከዕለት ወደ ዕለት እየተስተካከለና እየተሻሻለ መምጣቱን አቶ ሲራጅ አስታውቀዋል፡፡   

በተመሳሳይ በኦሮሚያ፣ በትግራይና በአማራ ክልል በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተለያዩ የፀጥታ ችግሮች እንደታዩባቸውና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለመቆጣጠርም የፌደራል የፀጥታ አካላት ከክልል የፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው መስራታቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከአካባቢዎቹ የአገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች ጋር በመሆን በተሰራው የጥበቃ፣ የውይይትና የመግባባት ስራዎች ከሦስት ያህል ዩኒቨርሲቲዎች ውጪ የመማር ማስተማር ሂደቱ በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛል ሲሉም ነው ያብራሩት፡፡  

በኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል የነበረ ግጭት ጋር ተያይዞ የነበረውን ስራ በተመለከተም የፀጥታ አካላቱ ግጭቱ ካለባቸው አዋሳኝ ቦታዎች የሁለቱንም ክልሎች የፀጥታ አካላት ነፃ እንዲሆን በማድረግ የፌደራል ፀጥታ አካላት እንዲሰፍሩ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም አንፃራዊ መረጋጋትና በሕዝቦች መካከል የተሻለ መቀራረብ ሊፈጠር ችሏል ብለዋል፡፡

ዘላቂ መረጋጋትን በተመለከተ ‹‹አሁንም በርካታ የሚቀሩ ስራዎች አሉ›› ያሉት ሚኒስትሩ፤ በተለይም ችግሮች በነበሩባቸው አካባቢዎች ሕገወጦችን በቁጥጥር ስር በማዋል በኩል ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

 አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ሕገወጥ ሰልፎችና ግጭቶችን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር አጠቃላይ የፖለቲካው ስራ ተጠናክሮ መስራቱ እንዳለ ሆኖ የፀጥታ አካላትም ችግሩን ሙሉ በሙሉ ከመቆጣጠር አንፃር በማያዳግም መልኩ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡          

የዚህን ዜና ዝርዝር በነገው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ይመልከቱ።

ብሩክ በርሄ

Published in የሀገር ውስጥ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።