Items filtered by date: Thursday, 01 February 2018
Thursday, 01 February 2018 18:07

ከስታዲየም ወደ ቤተመንግስት

ለዓመታት በእግር ላይ ጎል በማስቆጠር የአለም ኮከብነት ማዕረግን ተጎናፅፏል፡፡ እግር ኳስን በሚገባ አጣጥሟል፡፡ እስከ ዛሬ ካስቆጠራቸው ጎሎች የተለየውን ግብ ደግሞ በቅርቡ በማስቆጠር የዓመታት ህልሙን እውን አድርጓል፡፡ ብቸኛው አፍሪካዊ የፊፋ ባለንዶር ባለ ክብር ጆርጅ ዊሃ፡፡ ዊሃ ፖለቲካውን ከተቀላቀለ ቢከራርምም፤ አዲሱ የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት በመሆን ቃለ መሃላ የፈፀመው ከሳምንት በፊት ነበር፡፡ በሞንሮቪያ ስታዲየም በተካሄደው ቃለ መሃላ ሥነ ስርዓት ላይ ለተሰበሰበው ሕዝብ ‹‹ለበርካታ ጊዜያት ስታዲየም ውስጥ ተገኝቻለው፤ የዛሬው ግን ከሌሎቹ ጊዜያት እጅግ የተለየ ነው›› ብሎ ነበር፡፡
ዊሃ በንግግሩ፤ ሃገሪቱ ላሉባት ችግሮች ‹‹ፈጣን መፍትሄ አመጣለሁ›› ብሎ ቃል ለመግባት እንደማይችል፤ ነገር ግን ላይቤሪያዊያን ወደሚያልሟቸው ግቦች ለመድረስ ፈጣን እርምጃዎችን እንደሚወስድ አስታውቋል። አገሪቱን በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ ለቆዩትና መንበረ ሥልጣኑን ላስረከቡት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡ ምክንቱም የቀድሞዋ ፕሬዚዳንት ከአውሮፓውያኑ 1944 ወዲህ ላይቤሪያ ውስጥ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተደረገ ምርጫ የስልጣን ሽግግር ሲደረግ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ አገሪቷን ወደ ተሻለ ፖለቲካዊ መረጋጋት ላመጧት የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍም ያለውን ከፍተኛ አድናቆትና ክብር አሳይቷል፡፡
ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ህብረት 30ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የታደመው ዊሃ ከሕብረቱ የዘንድሮ መሪ ቃል ጋር የሚጣጣም ዕቅድ አለው፡፡ ምክንያቱም ዊሃ በቃለ መሃላው ወቅት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ትላልቅ ጉዳዮች መካከል ሙስናን መዋጋት አንዱ መሆኑን አስታውቆ ነበር፡፡ የፕሬዚዳንትነት ሕይወቱን በቅርቡ ‹‹ሀ›› ብሎ የጀመረው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዊሃ የእግር ኳስ ሕይወትና ፖለቲካዊ ጉዞውን በወፍ በረር እንቃኛለን፡፡
ሙሉ ስሙ ጆርጅ ታውሎን ማኔህ ኦፖንግ ሆስማን ዊሃ ይሰኛል፡፡ ከዛሬ 51 ዓመት በፊት እ.አ.አ ጥቅምት አንድ ቀን 1966 ነበር ይህቺን ዓለም የተቀላቀለው፡፡ በላይቤሪያ መዲና ሞንሮቪያ ክላራ በተሰኘ ጎስቋላ መንደር ተወልዶ ያደገው ዊሃ ቤተሰቦች ክሩ የተባለው ጎሳ አባል ናቸው፡፡ በላይቤሪያ ደቡብ ምስራቅ የሚገኙት እነዚህ ጎሳዎች እጅግ በጣም ደሃ የሚባል ኑሮን ለመግፋት ተገደዋል፡፡ አባቱ ዊሊያም በመካኒክነት ሙያ ሲያገለግሉ፤ እናት ሃና ኩዬ በአነስተኛ ንግድ ውስጥ ይገኙ ነበር፡፡
ዊሊያም፣ ሞሰስ እና ዎሎ የተባሉ ሶስት ወንድሞች አሉት፡፡ የእናትና አባቱ እህል ውሃ በፍቺ ሲደመደም ገና ህፃን የነበረው ዊሃ፤ ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በሙስሊም ኮንግረስ፤ ሁለተኛ ደረጃን በዌልስ ኤሪስተን ተከታትሏል፡፡ ነገር ግን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሊያጠናቅቅ አንድ አመት ሲቀረው አቋርጦ በመውጣት የኋላ ኋላ ለዝና ያበቃውን እግር ኳስ ጀመረ፡፡
የእግር ኳስ ሕይወቱን የጀመረው ከ15 ዓመት በታች የሚገኙ ታዳጊዎች በሚጫወቱበት አነስተኛ ቡድን ውስጥ ነበር፡፡ በቡድኑ ባሳየው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ዊሃ ባሕር ተሻግሮ የእግር ኳስ ሕይወቱን በፕሮፌሽል ደረጃ ለማሳደግ ተዘጋጀ፡፡ ነገር ግን ዕድል ካልተጨመረበት በስተቀር እንኳንስ በዚያ ዘመን አሁንም ድረስ ያንን ዕድል ለማግኘት ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላልና ጉዞው ቀላል አልሆነም፡፡ ይሄን ከማሰቡ በፊት ግን በአገሩ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ቴክኒሻን በመሆን አገልግሏል፡፡ ዊሃ ከአገሩ ጋር ለአህጉራዊ ዋንጫ ክብር ባይበቃም ሁለት ጊዜ ከላይቤሪያ ጋር በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፏል፡፡
ጆርጅ ዊሃ የእግር ኳስ ተጫዋችነት ሕይወቱን በማስቀጠል በላይቤሪያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ማንሳት ችሏል፡፡ በአገር ውስጥ ሊግ ባሳየው ከፍተኛ የእግር ኳስ ብቃትም የወቅቱ የካሜሮን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ክላውድ ሊሮይ ለአሁኑ የመድፈኞቹ አሰልጣኝ አርሴን ቬንገር ጠቆሟቸው፡፡ በወቅቱ ሞናኮን እያሰለጠኑ የነበሩት ቬንገር እ.አ.አ 1988 ዊሃን በ12ሺ ፓውንድ አስፈረሙት፡፡ የጆርጅ ዊሃ የእግር ኳስ ኮከብነት ጎዳናም መጠረግ የጀመረው ከዚህ ጊዜ አንስቶ ነበር፡፡
ሞናኮን በተቀላቀለ በዓመቱ የአፍሪካ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ለመመረጥ የበቃው ዊሃ፤ ከሁለት ዓመት በኋላ የፈረንሳይ ሊግ ዋንጫን ሲያነሳ፤ እ.አ.አ 1992 በአውሮፓ የክለቦች ዋንጫ እስከ ፍፃሜ መድረስ ችሏል፡፡ በዚህ ውድድርም በዘጠኝ ጨዋታዎች አራት ጎል ማስቆጠር ችሏል፡፡ በቀጣዩ ዓመት ዊሃ ከሞናኮ ወደ ፈረንሳዩ ታላቅ ክለብ ፒ.ኤስ.ጂ ተዘዋወረ፡፡ የፓሪሱ ክለብ እንደዛሬው በአረብ ባለሃብቶች ጡንቻው ከመፈርጠሙ በፊት አፍሪካዊው ኮከብ የክለቡ ኮከብ ለመሆን በቅቶ ነበር፡፡
ክለቡን በተቀላቀለ በሁለት ዓመቱ የፈረንሳይ ሊግን ማንሳት ችሏል፡፡ በ1994/95 የውድድር ዘመን የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ኮከብ ጎል አስቆጣሪ የሆነው ዊሃ፤ ይሄን ተከትሎ ፊቱን ወደ ጣሊያን በማዞር ለኤሲ ሚላን ፈርሟል፡፡ ዊሃ ትልቅ ዓለም አቀፋዊ ዝና ያጎናፀፈውን የዓለም ኮከብ ተጫዋችነት ክብርን የተጎናፀፈውም በዚሁ ክለብ ነበር፡፡ በኤሲ ሚላን በነበረው የአራት ዓመታት ስኬታማ ቆይታ ሁለት ጊዜ የሴሪያው የሻምፒዮንነት ክብርን ከክለቡ ጋር ከፍ አድርጓል፡፡
በዝናው ጀምበር ማዘቅዘቅ ወደ እንግሊዝ በመጓዝ ለቼልሲ እና ለማንቸስተር ሲቲ የተጫወተው ዊሃ በልጅነቱ የአውሮፓን ምድር እንዲረግጥ ምክንያት የሆኑትን አርሴን ቬንገር በተቃራኒ ቡድን መለያ ገጥሟል፡፡ በመጨረሻም አውሮፓን ቀድሞ ወደረገጠባት ፈረንሳይ በማቅናት እ.አ.አ 2001 ለማርሴይ ፊርማውን አኑሯል፡፡ ከሁለት ዓመት የፈረንሳይ ቆይታው በኋላም ፊቱን ወደ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ በማዞር ለአልጀዚራ ክለብ ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡
ዊሃን በተመለከተ ‹‹ከእግር ኳስ ተጫዋችም በላይ›› ሲሉ የሚያሞካሹት አድናቂዎቹ በተለይም እ.አ.አ 1995 የአፍሪካ፣ የአውሮፓና የዓለም ኮከብነትን በመጠቅለል ከአህጉሩ አንዱና ብቸኛው ባለታሪክ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡ ይሄ ክብር ለዊሃ ዓለም አቀፋዊ ዝና በር ከመክፈት አልፎ በእርስ በእርስ ጦርነት አብዝቶ የሚታወቀውን የአገሩን ስም በበጎ ለማስጠራት የሚችልበትን ዕድል እንዲያስብ በር ከፍቶለታል-ፖለቲካ፡፡
ስፖርት ከማዝናናቱ ባሻገር ለበርካታ ፖለቲከኞች መፈጠር ምክንያት የሚሆን ዘርፍ መሆኑ በብዙዎች ዘንድ ይመሰከራል፡፡ የበርካታ ፖለቲከኞች የስፖርቱ ዓለም ተሳትፎም ለዚህ ማሳያ ይሆናል፡፡ በአገሩ ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ግጭት መጠናቀቅ ተከትሎ ወደ ፖለቲካ ሕይወት የመቀላቀል ህልም እንዳለው ያሳወቀው ዊሃ፤ እ.አ.አ 2005 በአገሩ በሚካሄደው ምርጫ ላይ እንደሚሳተፍ አሳወቀ፡፡ በእርግጥ ኮከቡ በአገሩ ለፕሬዚዳንትነት የሚበቃ ተወዳጅነትና ተቀባይነት ባይጎድለውም ለመሪነት የሚበቃ የትምህርት ዝግጅት የሌለው መሆኑ በምርጫ ፉክክሩ ፈተና ሆኖበት ነበር፡፡ ምክንያቱም በተቃራኒው የሚፎካከራቸው የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ናቸውና፡፡
በመሆኑም የቀድሞው የእግር ኳስ ኮከብ በቀድሞዋ የዓለም ባንክ ተቀጣሪ ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ ለመሸነፍ ተገዷል፡፡ በዚህ ምርጫ ተስፋ ያልቆረጠው ዊሃ እ.አ.አ 2011 በተካሄደው ምርጫ ቢወዳደርም አሸናፊ መሆን አልቻለም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ዊሃ በትምህርቱ ብዙም አልገፋም ነበር፡፡ በመሆኑም ደካማ ጎኑን ለመቅረፍ ወደ ሚያሚ በማቅናት በዴቭሪይ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድምንስትሬሽን ዲግሪውን ተቀብሏል፡፡
በመጨረሻም እ.አ.አ በ2017 በሚካሄደው የላይቤሪያ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ እንደሚወዳደር በመግለጽ ዳግም ወደ ፖለቲካው ተመለሰ፡፡ በመጀመሪያው ዙር 38 ነጥብ አራት በመቶ ድምፅ በማግኘት ያሸነፈ ሲሆን፤ በሁለተኛው ዙር ምርጫ 60 በመቶ ድምፅ በማግኘት በፅኑ ሲፈልገው የነበረውን የፕሬዚዳንትነት ውድድር በማሸነፍ የቤተመንግስቱን ቁልፍ ሊረከብ ችሏል፡፡ በዚህ መልኩ ዊሃ ከእግር ኳስ ኮከብነት ወደ ርዕሰ ብሔርነት ተሸጋግሯል፡፡ በቤተመንግስት ቆይታውም ከወርሃዊ ደመወዝና ጥቅማጥቅም 25 በመቶ ለመቀነስ ወስኗል፡፡

ብሩክ በርሄ

Published in ስፖርት

ከአትሌቲክስ ስፖርት ጋር ስሟ ተያይዞ የሚነሳው ኢትዮጵያ፤ ታዋቂ የሆነችው በተለይ በረጅም ርቀት የመምና የጎዳና ላይ ሩጫ ነው። በአንጻሩ በአጭር ርቀት፣ በሜዳ ተግባራት እና በርምጃ ስፖርቶች ጎልቶ የሚነሳ ዝና የላትም። በዓለምና አህጉር ዓቀፍ ውድድሮች ላይም በእነዚህ ስፖርቶች የምታስመዘግባቸው ውጤቶች እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም።
ይህንኑ ስፖርትም ለማሳደግና ለማበረታታትም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በክለቦች መካከል የሚካሄድ ዓመታዊ ሻምፒዮና ያዘጋጃል። የዘንድሮው ክለቦችንና የማሰልጠኛ ተቋማትን የሚያሳትፈው ውድድርም በአዲስ አበባ ስታዲየም ትናንት ተጀምሯል። በውድድሩ ላይም የአጭር ርቀት፣ የመካከለኛ ርቀት፣ የ3ሺ ሜትር መሰናክል፣ ሪሌ፣ ርምጃ፣ ውርወራ እና ዝላይ፤ በአጠቃላይ በሴትና በወንድ 40 የውድድር ተግባራት ተካተዋል።
የዚህ ውድድር መካሄድም የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላት የአጭርና መካከለኛ ርቀት፣ የሜዳ ተግባራት እንዲሁም የርምጃ ተወዳዳሪዎቻቸውን አቋም ለመፈተሽ ያስችላቸዋል። በዚህ ርቀት አለም ዓቀፍም ሆኑ አህጉር አቀፍ ውድድሮች የመዘጋጀት ዕድላቸው አናሳ በመሆኑ ለክለቦችና ማሰልጠኛ ማዕከላት የውድድር መድረክም ለመፍጠር ታስቦም ነው የሚካሄደው። በክለቦች መካከል ውድድር በማካሄድ ያሉበትን አቋም እንዲመለከቱ እንዲሁም ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል። በውድድሩ ላይም ከ30 ክለቦችና የስፖርት ማሰልጠኛ ተቋማት 650 የሚሆኑ አትሌቶች እየተሳተፉበት ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ፤ ውድድሩ ሃገር ዓቀፍ እንደመሆኑ መልካም የሚባል ቢሆንም፤ ለአህጉርና ዓለም ዓቀፍ ውድድር ግን ብዙ የሚቀር መሆኑን ይገልጻል። በተለይ በመሰል ውድድሮች ላይ የተወዳዳሪዎችና የተመልካቾች እጥረት ይታያል። ውድድሩ ሃገሪቷ በርቀቶቹ ያለችበትን ደረጃ የሚያሳይ ሲሆን፤ ጉድለቶችን በመመልከትም ለማስተካከል የሚሰራ ይሆናል። በተለይ ተወዳዳሪዎቹ እንደየስፖርት ዓይነቱ ከሰውነታቸው ጀምሮ አመራረጣቸው ምን ይመስላል የሚለውንም ለመገምገም ይረዳል። ከዚህ በመነሳትም ፌዴሬሽኑ ባዘጋጀው የስልጠና ማኑዋል ወደ ስራ የሚገባ መሆኑን ያስረዳል።
የተመልካች ድርቅ በታየበት የመጀመሪያው ዕለት በርካታ ውድድሮች የተካሄዱ ሲሆን፤ በዲስከስ ውርወራ ወንድና ሴት፣ በርዝመት ዝላይ ሴት እንዲሁም በሴቶች የ3ሺ ሜትር መሰናክል ውድድሮች ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። በውጤቱ መሰረትም፤ የፌዴራል ማረሚያዋ ወይንሸት አንሳ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዋ መስታወት አስማረ እንዲሁም የጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ ማዕከሏ ቤተልሄም ሙላት እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ በመያዝ የ3ሺ ሜትር መሰናክል ውድድርን ያጠናቀቁ አትሌቶች ሆነዋል።
በወንዶች የዲስከስ ውርወራ የሲዳማ ቡናዎቹ ለማ ከተማ እና ማሙሽ ታዬ የወርቅና የነሃስ ሜዳሊያውን ሲወስዱ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አትሌቱ ገበየሁ ገብረእየሱስ ደግሞ ሁለተኛ በመሆን የሜዳሊያ ሽሚያው ውስጥ ገብቷል። በሴቶች የዲስከስ ውርወራ የንግድ ባንክ አትሌቶች መርሃዊ ጸሃይ እና አለሚቱ ተክለስላሴ አንደኛ እና ሶስተኛ ሲሆኑ፤ የሲዳማ ቡናዋ ዙርጋ ኡስማን ደግሞ የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች። ሌላኛው የፍጻሜ ውድድር የተካሄደበት የሴቶች ርዝመት ዝላይ ነው። በዚህ ውድድር ላይም የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ አራያት ዲቦ የበላይነቱን ስትይዝ የመከላከያዋ ኡጁዳ ኡመድ እና የሲዳማ ቡናዋ ጊጎስ ቱቃ እስከ ሶስት ባለው ደረጃ ውድድራቸውን ፈጽመዋል።
ዛሬ ቀጥሎ በሚውለው የሁለተኛ ቀን መርሃ ግብርም፤ የሴቶች ከፍታ ዝላይ፣ የሴቶችና ወንዶች 100 ሜትር፣ የወንዶች አሎሎ ውርወራ፣ 800 ሜትር የወንዶችና ሴቶች፣ የጦር ውርወራ ወንዶች፣ 400ሜትር ወንድና ሴት፣ 100ሜትር መሰናክል ሴት፣ 4በ1ሺ500ሜትር ድብልቅ እንዲሁም የ110ሜትር መሰናክል ወንዶች የፍጻሜ ውድድሮች የሚካሄዱ ይሆናል። ውድድሩ እስከ መጪው እሁድ 27/05/2010ዓም በአዲስ አበባ ስታዲየም ቀጥሎ የሚካሄድም ይሆናል።
በውድድሩ ላይ አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች እንደየደረጃቸው የሜዳሊያና የገንዘብ ሽልማት የሚበረከትላቸው ሲሆን፤ በቡድን ነጥብ አሸናፊዎች በሁለቱም ጾታዎች የዋንጫ እንዲሁም የሴትና የወንድ ነጥብ ተደምሮ በአጠቃላይ የቡድን አሸናፊ የዋንጫ ሽልማት ያገኛሉ።

ብርሃን ፈይሳ

 

Published in ስፖርት

ግብፅ የቱሪዝም ዘርፏን ለማሳደግ የዓለማችንን ረጅሙን ቱርካዊ ኮሰን እና አጭሯን ህንዳዊቷ ጂዮቲ አምጌን ጋብዛ የተለያዩ መስህቦቿን ማስጎብኘቷን ሰሞኑን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡ የ36 ዓመቱ ኮሰን ሁለት ሜትር ከ50 ሳንቲ ሜትር፤ በተቃራኒው የ25 ዓመት ህንዳዊት የዓለም አጭሯ ሴት አምጌ 62 ነጥብ ስምንት ሳንቲ ሜትር ትረዝማለች፡፡ ዛሬ ደግሞ ከአገራችን መለሎ አስራት ፋና በኋላ ብቅ ካሉት መካከል አንዱን ለግላጋ እናስተዋውቃችሁ፡፡ ቁመቱ 2 ሜትር ከ22 ሳንቲ ሜትር የሆነው አስራት ኑሮውን በውጭ አገር ያደረገ ሲሆን፤ ይህ ወጣት እርሱን ይተካ ይሆን ? የሚለው ጥያቄ ማረጋገጫ ይሻል፡፡
ነገዎ ጂማ ይባላል፡፡ የ24 ዓመቱ ወጣት ተወልዶ ያደገው መቂ ከተማ ነው፡፡ ቁመቱ ሁለት ሜትር ከአምስት ሳንቲ ሜትር ይደርሳል፡፡ ‹‹የቤተሰቦቼ ቁመት ረጃጅም የሚባል አይደለም›› የሚለው ነገዎ፤ የታላቅ ወንድሙ ቁመት ረጅም የሚባል ዓይነት ቢሆንም የእርሱ ይሄን ያህል የተጋነነ መሆኑ ምስጢር ግልፅ እንዳልሆነለት ይናገራል፡፡ ወደ አዲስ አበባ ብቅ ያለው በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሲያሰቃየው ከሰነበተው የጭንቅላት ዕጢ ለመፈወስ ሲሆን፤ በእዚያ ክትትል በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ‹‹ድሮ ደህና ነበርኩ›› የሚለው ወጣቱ፤ አሁን አሁን ግን ሲራመድ እግሩን ያመዋል፡፡
ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ህመሙ እንደጀመረው የሚናገረው ነገዎ፤ ድንገት እየጣለው ስለተቸገረም ምርኩዝ ከመደገፍ በተጨማሪ እርምጃውም በዝግታ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ከቁመቱ ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች እንደ ቅርጫት ኳስና ቮሊቦል የመሳሰሉ ስፖርታዊ ጨዋታዎችን እንዲያዘወትር ይጋብዙታል፡፡ እርሱ ግን ጤናው በሚገባ ከተመለሰለት እንደማንኛውም ሰው ሰርቶ ራሱን የመለወጥ ዕቅድ አለው፡፡
‹‹የአዲስ አበባ ቤት ኪራይ ከብዶኛል›› የሚለው ወጣቱ፤ ሊያስታምሙት የመጡት አባቱም ተመልሰው ወደ አገራቸው መጓዛቸውን ያወጋል፡፡ አሁን ብቻውን ኑሮን ይገፋል፡፡ ሰዎች መንገድ ላይ ሲያዩት እንደሚገረሙና የእርሱን ቁመት እንደሚመኙ ይገልጹለታል፡፡ ትምህርቱን መከታተል የቻለው እስከ ሰባተኛ ክፍል ድረስ ነው፡፡ ከዚያ በላይ ለመቀጠል ቢፈልግም ከህመሙ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ችግር ስለገጠመው አቋርጦታል፡፡ ወደፊት ትምህርቱን የመቀጠል ፅኑ ፍላጎት አለው፡፡ በኢትዮጵያ ካንተ የሚበልጥ ረጅም ሰው አለ? ለሚለው ጥያቄ ‹‹አስራት የሚባል ረጅም ሰው መኖሩን ሰምቻለው፤ ግን አይቼው አላውቅም›› ይላል፡፡ ወጣቱ ልብስ ባይቸገርም የጫማ ጉዳይ ሁሌም ያሳስበዋል፡፡

ብሩክ በርሄ

Published in መዝናኛ
Thursday, 01 February 2018 17:57

የሃሳብ አብሾ

ከበጣም መጥፎ ይሻላል መጥፎ እንደሚባለው፤ አብሾ ካለበት ሰካራም ጤናማ ሰካራም ይሻለኛል፡፡ መቼስ… አንድ ሰው ሰክሮ የወትሮ አመሉን ባለበት መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ አብሾ ተጨምሮበት አስቡት እስኪ፡፡ ለነገሩ ዙሪያችንን ብንቃኝ በዕለት ተዕለት ሕይወቱ በመንደርተኛው ዘንድ በሰው አክባሪነቱ የሚመሰገን ሰው ጥኑ የመጎንጨት አመል ካለበት፣ ቀን ሌላ ምሽት ሌላ መሆኑ አይቀርም፡፡ ሰው ሲጠጣ ምላሱም ራሱም ይተሳሰራል፡፡ አረማመዱም አስተሳሰቡም ይወላገዳል፡፡ ምክንያቱም ይሄ የስካር መገለጫ ባሕሪ ነው፡፡
ውይ… ስካር ብል ተክሌ ትዝ አለኝ፡፡ ጎልማሳው ተክሌ ሰፈራችን ካሉ ጠጪዎች በአሰካከሩ ይለያል፡፡ አቤት! ይጠጣዋል፡፡ እንዲያውም በአሰካከሩ የሚቀኑ ብዙ አጣጪዎች እንዳሉት ሰምቻለሁ፡፡ አስቡታ… በስካር ሲቀና፡፡ በእርግጥ የሚቀኑበት ወደውም አልነበር፡፡ ተክሌ ‹‹ማገዶ አይፈጅም›› የሚሉት አይነት ወጪ ቆጣቢ ሰካራም ነው፡፡ ሁለት ብርሌ ከቀመሰ ምላሱ ይተሳሰራል፤አናቱን መሸከም ይከብደዋል፡፡ የሚገርመው ግን ተክሌ በጤናማ ባሕሪው (በተለይ ቀን ቀን) ከመንደሩ ነዋሪ ጋር ተግባብቶና ተከባብሮ የሚኖር፣ ለቅሶ ደራሽ፣ የታመመ ጠያቂ፣ ያለውን አቋዳሽ ቅን ሰው ነው፡፡ ብቸኛ ችግሩ ፈሳሽ ማዘውተሩ ነው፡፡
ይሄን ባሕሪውን ጠንቅቀው የሚያውቁ እትዬ ውብነሽ (የጠጅ ቤቱ ባለቤት) ተክሌ ኮታውን ሲያልፍ አንጋፋውን ጠጅ ቀጂ ክብሩን ይጠቅሱታል፡፡ ደንበኞች ክብሩን ሲያደንቁት ከአንድ ሜትር ርቀት ጠጅ ቢያንቆረቁር የብርሌን ከንፈር አይስትም ይሉታል፡፡ አንዳንዴ ታዲያ እርሱን ነበር'ጂ ዳርት ማጫወት ስል አስባለሁ፡፡ ለማንኛውም እትዬ ውብነሽ በአንድ አይናቸው የሚንገዳገደውን ተክሌ በሌላኛው ክብሬን እየተመለከተ (በጣም ይወዱታል) ‹‹ና ወዲህ›› ይሉታል፡፡ ‹‹ነገር'ኩ ከዚህ በኋላ ለተክሌ እንዳትደግመው›› ቀጭኗን ትዕዛዝ ተቀብሎ ይተገብራል፡፡ ይኸን ትዕዛዝ ተከትሎ በቤቱ ጭቅጭቅ መንገስ ይጀምራል፡፡
እትዬ ውብነሽ ይሄን ማድረጋቸው ገበያ በመጥላት ወይም ለተክሌ በማሰብ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁኑም… ተክሌ ኮታውን ካለፈ በደቂቃዎች ልዩነት ጠጅ ቤቱ ወደ ጦር አውድማ ሊቀየር ይችላል፡፡ የምሽት ዜና የሚያዩትን ይረብሻል፡፡ በተለይ አቶ መካሻ በዜና የመጣባቸውን ሰው በቀልድ አይፋቱም፡፡ በሁለቱ መካከል ግጭት ይቀሰቀስና ወደሁሉም ጠጪ ይሸጋገራል፡፡ ተክሌ አቅም ባይኖረውም ይፍጨረጨራል፡፡ ትኩር ብሎ ያየውን ሰው ሳይቀር ትከሻ እየጎነተለ ‹‹ምን ታፈጣለህ? እኔ ተክሌ ማንንም አልፈራ…›› ይላል፡፡ የስካር ስቅታ እያጨናነቀው ‹‹…ባታውቀኝ ነው ማንነቴን!›› እያለ ጠጪውን ሰላም ይነሳል፡፡ በቃ ያዙኝ ልቀቁኝ ነው፡፡
እንዲህ የሚሆነው ወ'ዶ አይደለም፤ ሲጠጣ አብሾ አለበት፡፡ የደርግ ዘማች ወታደር የነበረ ቢሆንም በጦር ከቆሰለው የሰውነቱ ክፍል ይልቅ በስካር አብሾ ያጎደላቸው ጥርሶቹ ብዙ ይናገራሉ፡፡ የሚገርመው ደግሞ ማታ ያደረገውን ጠዋት መርሳቱ ነው፡፡ እንዲያው ዝም ብዬ ሳስተውል… አሁን ላይ ሳይጠጡ ነገር ግን በባሕሪ ተክሌን ሲመስሉ የማያቸው ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ የዘመናችን አንደኛው ትልቁ በሽታ ልክ ተክሌ ሲጠጣ አብሾ እንደሚነሳበት ሁሉ ሚሪንዳ እየጠጡ በአንድ ጉዳይ ላይ የሃሳብ ክርክር ሲነሳ ድብቅ አብሿቸው ገንፍሎ የሚወጣ ሰዎች እየበዙ መምጣታቸው ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ልክ እንደ ተክሌ የተከበሩም ሰው አክባሪም ናቸው፡፡ ነገር ግን ክርክር ሲነሳ ልውጥ ይላሉ፡፡ በውስጣቸው ተሟግቶ የመርታት ጉልበት ያለው ጠቃሚ ሃሳብ ቢኖራቸውም ቶሎ ብግን ይላሉ፡፡ ያነጋገር ቅላፄያቸው ከመቅፅበት ከእርጋታ ወደ ቁጣ ይቀየራል፡፡ መናገርን እንጂ ማድመጥ አይፈልጉም፡፡
እንዲህ አይነት ዝንባሌ ማህበራዊ ድረ ገፅንም ያጥለቀለቀ ክፉ አመል ሁኗል፡፡ ሰዎች የግል ፖለቲካዊ አቋማቸውን ሲያንፀባርቁ ልዩነትን አክብሮ ከመቀበል ይልቅ ሚዛን ያጣ ውግዘት የሚያደርሱ ጥቂት አይደሉም፡፡ እንዲህ አይነት ሰዎች ‹‹እኔን ካልመሰልክ…›› በሚል ግብዝነት ብቻ መልካም ወዳጃቸውን ያሳዝናሉ፡፡ ይሄ ደግሞ በሰዎች ሃሳብ ውስጥ ያለ አብሾ ነው፡፡ ስልጡን ናቸው፤ የተማሩ ናቸው የሚባሉ ሰዎች የሃሳብ ብዙሕነት መኖሩን ባይክዱም መቀበል ግን ይከብዳቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ለቆሙለት ፖለቲካዊ አመለካከት የሚመጥን ቁመና ሲያጡ ይታያል፡፡
በማህበራዊ ሕይወታቸው ምስጉን የሆኑ ሰዎች በማህበራዊ ድረገፅ ላይ ክፉኛ የሚያስወቅሳቸውን ተግባር ሲፈፅሙ ይታያሉ፡፡ በሕዝብ መካከል መዋደድንና መከባበር እንዲሰፍን ከመስበክ ይልቅ ዘረኝነትን ለማስፋፋት ሲታገሉ ይታያል፡፡ ይሄ አብሾ ነው፡፡ ሁለት ማንነት…፡፡ ልክ እንደ ተክሌ ጠዋት ሌላ ማታ ሌላ፡፡ ተክሌ ጠጅ ቤት ሄዶ ባሕሪው ሲቀየር እንዲህ ያሉት ሰዎች ድረገፅን መሸታ ቤት ያደርጉታል፡፡ ጣታቸው የፊደል ገበታ ሲጫን በጎ ሰብዕናቸው ይለወጣል፡፡ እንዲህ አይነት ሰዎች በነባር ማንነታቸው ቢቀጥሉ ወይም የሃሳብ ልዩነታቸውን በአግባቡና በኃላፊነት ቢያሰፍሩ በእነርሱ አመክንዮ ብዙ ባስተማሩ ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡
ሰዎች ምንም አይነት አመለካከት ይኑራቸው፤ ነገር ግን ይሄን ልዩነታቸውን በክርክር ማሟሸት እየቻሉ ወዳለመግባባት ይገባሉ፡፡ በየትኛውም መመዘኛ ያለመግባባት ውጤቱ ጤናማ ሊሆን አይችልም፡፡ ከአንደኛው ጥግ ቆሞ ‹‹እርሱ ወደኔ ካልመጣ አልንቀሳቀስም›› በሚል ግትርነት መቀራረብ አይፈጠርም፡፡ መቀራረብ ፍላጎት ይፈልጋል፡፡ ፍላጎት ደግሞ ምንጩ ብስለት ነው፡፡ የበሰለ ማንነት አማራጮችን ለአማራጮች በር አይዘጋም፡፡
አሁን አገራችን ላለችበት ወቅታዊ ችግር አንዱ ምክንያት በአግባቡ አለመደማመጥ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ችግሮቻችንን ጠንቅቀን ብናውቅም በችግሮቻችን ዙሪያ ተከራክረን ማለፍ ስለከበደን ጉዳያችን ይወሳሰባል፡፡ አንዱ የሌላውን ሃሳብ ሳያጣጥም የእርሱን ሃሳብ ማስተላለፍ አይችልም፡፡ ስለዚህ በተገኙት መድረኮች ሁሉ የመደማመጥ ባሕላችንን ማሳደግ ተገቢ ነው፡፡ ሃሳብ ለማላመጥ ‹‹ትክክል አይደለህም!›› ሲባል ‹‹እንዴት ትክክል አይደለህም እባላለሁ!?›› በሚል አብሾው የሚነሳ ሰው ለሃሳብ ሰጪውም ለተቀባዩም ማስቸገሩ ይቀጥላል፡፡ ለመደማመጥ ፍላጎት ያስፈልጋል፡፡ አገር የግለሰቦች ስብስብ ናት፤ ስለዚህ የሌላውን ሃሳብ አክብሮ መደማመጥ የግድ ይላል፡፡

ብሩክ በርሄ

Published in መዝናኛ

በኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ከ15-29 የሚገኙ ወጣቶች 34 በመቶውን የህዝብ ቁጥር እንደሚሸፍኑ ከወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡ ከአሃዛዊ መረጃው መረዳት እንደሚቻለው በዚህ የእድሜ ክልል የሚገኙ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡ የነገ ሀገር ተረካቢ እንደመሆናቸውም ማህበራዊ ተጠቃሚነትታቸውን ማረጋገጥ የዛሬዋን እና የነገዋን ኢትዮጵያ የተሻለች ማድረግ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
የወጣቱን ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከጤና ችግሮች እና ማህበራዊ ጠንቆች ሊያላቅቁ የሚችሉ አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ በተለይም የስነ ተዋልዶ ጤናን አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ዋነኛው ተግባር መሆን አለበት፡፡ በዚህ ረገድ በስነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ የሚሰሩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የተለያዩ ተግባራትን የሚያከናውኑ ሲሆን፤ ሰሞኑን ዲ ኤስ ደብሊዩ የተሰኘ ዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ከወጣት ማህበራት እና አጋር አካላት ጋር በመሆን እ.አ.አ በ2017 የወጣቶችን የስነ ተዋልዶ ጤና ለማሻሻል የሰራቸውን ስራዎች በጋራ መድረክ ገምግሟል፡፡
የዲ ኤስ ደብሊዩ ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ ፈየራ አሰፋ በዚህ መድረክ ላይ እንደተናገሩት፤ የድርጅቱ ዓላማ ወጣቶች እውቀት እና ክህሎት ኖሯቸው የወደ ፊት ሀገር ተረካቢ እንዲሆኑ እገዛ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ጤና ወሳኝ ነው፡፡ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ ላለፉት 17 ዓመታት የወጣቶችን የስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮችን ለመፍታት የበኩሉን ሲወጣ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከል ብሎም ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገትን በማፋጠን ሀገሪቱ የያዘችውን ዕቅድ ለማሳካት የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል፡፡
በተለይም የወጣቱን የስነ ተዋልዶ ጤና ለማሻሻል ወጣቱን በማብቃትና የህይወት ክህሎቱን እንዲያዳብር ለማገዝ የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ ሰርቷል፡፡ በዚህም ወጣቶች ራሳቸውን በማብቃት እና እርስ በእርሳቸው በመማማር በስነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ በራሳቸው እንዲወስኑ እና የአገልግሎቱም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ወጣት ለወጣት በሚል ፕሮግራም ሲሰራ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ፈየራ ማብራሪያ ድርጅቱ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ ብሄርና ብሄረሰቦች ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ 70 የወጣቶች ማህበራትና ክበባት ጋር ትስስር በመፍጠር እየሰራ ነው፡፡ ድርጅቱ የዛሬ 13 ዓመት በቢሾፍቱ ከተማ በገነባው ቦኒታ የወጣቶች ማሰልጠኛ ማዕከል የእነርሱ ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ ማኑዋሎችን በማዘጋጀት ስልጠና ይሰጣል፡፡ ወጣቶቹ በስልጠናው ያገኙትን እውቀት እና ክህሎት ወደ ተግባር ቀይረው ህይወታቸውን እና ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ ለማገዝ የፋይናንስ እና የቴክኒክ ድጋፍም ያደርጋል፡፡ የሰለጠኑ ወጣቶችም ወደ አከባቢያቸው ሲመለሱ ሌሎችን የማሰልጠን ሃላፊነት አለባቸው፡፡
በትምህርት ቤት፣ በስራ ቦታ እና ከትምህርት ቤት ውጪ ያሉ ወጣት ማህበራትና ክበባት ወጣቶች የተዋልዶ ጤና አገልግሎት እንዲያገኙ በየአካባቢው ካሉ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩ እገዛም እያደረገ ነው፡፡ ከዚያ አልፎም የጤና ባለሙያዎች ለወጣቱ ምቹ የሆነ የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል ለጤና ባለሙያዎች ስልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑንም አቶ ፈየራ አብራርተዋል፡፡
እንደ አቶ ፈየራ ማብራሪያ በአሁኑ ወቅት በትምህርት ገበታ ያሉ ወጣቶችን በሙያ እና በስነ ምግባር ኮትኩቶ በማሳደግ ረገድ የመምህራን ሚና የጎላ ነው፡፡ መምህራን ይህን ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለሚገኙ መምህራን እገዛ ያደርጋል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በስራ ቦታ የሚገኙ ወጣቶችን የስነ ተዋልዶ ጤና ሁኔታ ለማሻሻል የስራ ቦታ የወጣቶች የስነ ተዋልዶ ጤና መርሃ ግብር ተቀርጾ እየተተገበረ ነው፡፡ ይህንን በተሳካ ሁኔታ ለመስራት ያስችል ዘንድ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ነው ያብራሩት
አቶ ፈየራ እንደሚሉት እ.አ.አ በ2017 ሀገሪቷ የነበረችበት ሁኔታ በወጣቶች ላይ ለሚሰሩ ስራዎች ብዙም አመቺ ያልነበረ ቢሆንም ከመንግስት መዋቅር እና ከወጣቶቹ ቅንጅት በመፍጠር የተቻለውን ያህል ጥረት ተደርጓል፡፡ ይህም በፕሮግራሙ ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ቢያሳርፍም ወጣት ማህበራትና ክበባት ባሳዩት ቆራጥነት ጥሩ ውጤት ተመዝግቧል፡፡
ባለፉት 17 ዓመታት ከ4 ሺ በላይ የሚገመቱ ወጣቶች በአመራር፣ በስራ ፈጠራ፣ በስነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ ስልጠና መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ወጣቶች የራሳቸውን ህይወት በተሻለ አኳኋን ከመምራት አልፈው የወጣት ማህበራትን እና ፌዴሬሽኖችን እየመሩ መሆናቸውን የድርጅቱ ስኬት ነው ብለዋል፡፡
ድርጅቱ ፕሮግራሙን እየከለሰ እና እየፈተሸ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ፈየራ በክለሳ ወቅት የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን እንደግብዓት በመጠቀም የተሻለ ስራ ለመስራት ድርጅቱ ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
የፋይናንስ ችግር፣ በየጊዜው በመንግስት መዋቅር የሚደረጉ የመዋቅር እና የአመራር ለውጦችን ተከትሎ ለአዳዲስ አመራሮች እና መዋቅሮች ስለ ድርጅቱ ለማስተዋወቅ የሚሰሩ ስራዎች ድርጅቱን እያጋጠሙ ካሉ ችግሮች ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ነው ያነሱት፡፡ ይሁን እንጂ ድርጅቱ ስራዉን በማስፋፋት ወጣቶች መሰረታዊ የስነ ተዋልዶ ጤና መረጃዎችን በማግኘት እና ችግር ፈቺ የሆነውን የህይወት ክህሎት በመታጠቅ ለቀጣይ ህይወት እንዲዘጋጁ ድርጅቱ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የድርጅታቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሪት ጽጌሬዳ ዘውዱ እንዳሉት፤ በስነ ተዋልዶ ዙሪያ በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ በወጣቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ አዎንታዊ ለውጥ ማምጣት ከቻሉ ተቋማት አንዱ ዲ ኤስ ደብሊዩ ነው፡፡ በተለይም የስነ ተዋልዶ ጤና መረጃና ስልጠናዎችን በመስጠትና ራስን በማስቻል ፕሮግራሞቹ በርካታ ወጣቶችን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ የወጣት አደረጃጀቶችን በስልጠና፣ በቁስ እና በፋይናንስ በመደገፍ እና አቅም የማጎልበት ስራዎችን በመስራት በርካታ ማህበራትን ለፍሬ አብቅቷል፡፡
በስነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ የተመዘገቡ ስኬቶች እንደተጠበቀ ሆኖ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ወጣቶች ዘንድ ለኤች አይ ቪ ኤድስ የሚያጋልጡ ባህሪያት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ በመምጣታቸው የበሽታው ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ሳይባባስ የወጣቶች ግንዛቤ እና የባህሪ ለውጥ በማምጣት ላይ የሚሰሩ ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል አሁንም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ሁሉም የማህበረሰብ አካላት በወጣቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ማለትም ጫት፣ ሺሻ፣ ሀሺሽ እና የመሳሰሉትን እንዲሁም መጤ ባህሎችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ለማስወገድ በጋራ መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡
የቢሾፍቱ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የስራ እድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ዓለሙ ጎንፋ እንደተናገሩት ወጣቶች ከስነ ተዋልዶ ጤና ጋር በተያያዘ ትክክለኛ መረጃ እና እውቀት እንዲያገኙ ማድረግ ማስቻል የወደፊቱን ሀገር ተረካቢዎች በጽኑ መሰረት ላይ እንደማነጽ ይቆጠራል፡፡ በተለይ በዲጂታል መረጃ ዘመን ላይ ወጣቶች በማህበረሰብ እና በቤተሰብ ደረጃ ተቀባይነት ያለውን ባህሪ እና የአመለካከት ሁኔታ ማዳበር እንዲችሉ ተገቢውን መረጃዎች እና አገልግሎቶች ቀጣይነት ባለው መልኩ ማቅረብ መቻሉ ሀገራዊ ልማት ግንባታ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው፡፡
ዲ ኤስ ደብሊዩ በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኙ የወጣቶችን ክበባት በመደገፍ ወጣቶች የስነ ተዋልዶ ጤና መረጃ እንዲያገኙ እና በእውቀት ላይ የተመሰረተ የባህሪ እና የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጡ ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡ በከተማዋ ላይ ከሚያካሂዳቸው የልማት እንቅስቃሴዎች ጋር በተያያዘ ከተለያዩ የመስተዳድሩ ጽህፈት ቤቶች ጋር መልካም የሆነ አጋርነት እንዳለው በመግለጽ የሚተገብራቸውን ስራዎች በጋራ በማቀድ እና በመተግበር ውጤታማ ስራዎችን እያከናወነ ነው፡፡ በመሆኑም ድርጅቱ ለሚሰራቸው ስራዎች ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ወጣት ወጋየሁ አየለ በደቡብ ክልል በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ የሶዶ ሰላም ስነ ተዋልዶ እና ጸረ ኤድስ ማህበር ሰብሳቢ ነው፡፡ በ1989 ዓ.ም በአራት በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች የተመሰረተው ማህበር በአሁኑ ወቅት 49 አባላት አሉት፡፡ ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ በወጣት ለወጣት ፕሮግራም ዙሪያ ከዲ ኤስ ደብሊዩ ጋር እየሰራ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም እሱ እና ሌሎች የማህበሩ አመራሮች የስነ ተዋልዶ ጤናን ጨምሮ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ስልጠና አግኝተዋል፡፡
በስልጠናው ያገኙትን እውቀት እና ክህሎት ወደ አካባቢያቸው በመሄድ ሌሎች ስልጠናውን ያላገኙትን ያሰለጥናሉ፡፡ ለስልጠናው አስፈላጊውን ወጪ በዲ ኤስ ደብሊዩ እንደሚበረከት የተናገረው ወጋየሁ ይህን ስልጠና ያገኙ ወጣቶች በትምህርት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ፤ ለስነ ተዋልዶ ጤና ችግር አጋላጭ ከሆኑ አካሄዶች ራሳቸውን ማቀብ፤ የአቻ ግፊት መቋቋም እንዲሁም በስራ ራሳቸውን መለወጥ መቻላቸውን ይናገራል፡፡
ወጣት ወጋየሁ ግን አንድ ስጋት አለው፡፡ ማህበሩ ለረጅም ዘመን በውጭ ድርጅቶች ነው ሲደገፍ የኖረው፡፡ አሁንም በውጭ ድርጅቶች ይደገፋል፡፡ ይህ ደግሞ ማህበሩን ስጋት ላይ ጥሏል፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ድጋፋቸውን ቢያቋርጡ የማህበሩ ህሊውና አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ ማህበሩ የራሱን ሀብት መፍጠር ቢፈልግም እስካሁን አልተሳካለትም፡፡ አሁንም ግን የራሱ የሆነ ገቢ ማግኘ መንገዶችን በማፈላለግ ላይ መሆኑን ተናግሯል፡፡
በአማራ ክልል በህር ዳር ከተማ በ1996 የተመሰረተው ቡቃያ ጸረ ኤድስ እና ስነ ተዋልዶ ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሪት ጤናዬ ዓለሙ በቢሾፍቱ በሚገኘው ቦኒታ ዲ ኤስ ደብሊዩ ማሰልጠኛ ማዕከል በስነ ተዋልዶ ጤና፣ በስራ ፈጠራ እና በአመራር ዙሪያ ለሶስት ሳምንታት ስልጠናዎችን ወስዳለች፡፡ ከስልጠና መልስ ወደ ባህር ዳር ስትመለስ የማህበሩን አባላት ስታሰለጥን እንደነበር ገልጻለች፡፡
ስልጠናውንም በዋናነት በሱስ ለተጠቁት፣ ለሴተኛ አዳሪዎች እንዲሁም የተለያዩ ማህበራዊ ችግር ውስጥ ላሉት ወጣቶች ትሰጣለች፡፡ ስልጠናውን የወሰዱ በርካታ ወጣቶች ከሱስ እና ከሴተኛ አዳሪነት ህይወት ተላቀው በሌሎች ገቢ ማግኛ ስራዎች ላይ ተሰማርተዋል ትላለች፡፡ ወጣት ጤናዬ ስልጠናውን ለወሰዱት ፈተና በመስጠት በፈተናው የተሻለ ውጤት ያገኙትን አሰልጣኝ በማድረግ ሌሎች ወጣቶችን እንዲያሰለጥኑ እንደምታደርግ ነው ያብራራችው፡፡
ማህበሩ ከክፍለ ከተማ እና ከዲ ኤስ ደብሊዩ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን የምትናገረው ወጣት ጤናዬ ክፍለ ከተማው ጽህፈት ቤት እና መሰብሰቢያ አዳራሾችን በመፍቀድ ዲ ኤስ ደብሊዩ ደግሞ የፋይናንስ እና ቴክኒካል ድጋፎችን እያደረጉ ነው፡፡ አሁን ማህበሩ አቅም ገንብቷል የምትለው ወጣቷ ማህበሩ የተለያዩ ገቢ ማሰባሰቢያ ዘዴዎችን ስላመቻቸ ያለማንም ድጋፍ መንቀሳቀስ የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል ብላለች፡፡
ወጣት ጤናዬ ቡቃያን ጨምሮ በባህር ዳር አካባቢ በስነ ተዋልዶ እና ፀረ ኤድስ ዙሪያ የሚሰሩ ማህበራትን ችግሮች እንደሚያጋጥማቸውም አልሸሸገችም፤ የማህበሩ አባላት መመናመን፣ ፈቃድ በተፈለገው ሰዓት ያለማደስ እንዲሁም አልፎ አልፎ የአዳራሽ ችግር ያጋጥማል፡፡ በዚህም ምክንያት በጸረ ኤድስ እና ስነ ተዋልዶ ዙሪያ የሚሰሩ በርካታ ማህበራት ጠፍተዋል ትላለች፡፡

መላኩ ኤሮሴ

Published in ማህበራዊ

የዓድዋ ድል ለማሰብ እና ለማመን የሚከብዱ ጀብዱዎች በኢትዮጵያውያን ጀግኖች የተፈጸመበት ነው፡፡ ድሉ ለኢትዮጵያውያን ብቻም ሳይሆን በመላ ዓለም በቅኝ ግዛት ሲማቅቁ ለነበሩ ህዝቦች በተለይም ለጥቁር ህዝቦች የተስፋ ጭላንጭልን የፈነጠቀ ስለመሆኑ በርካታ የታሪክ ድርሳናት ይተርካሉ፡፡ ሆኖም ‹‹በእጅ ያለ ወርቅ…›› እንዲሉ ኢትዮጵያ የዚህን ትልቅ ድል ትሩፋቶች በአግባቡ ትጠቅመበታለች ወይም እየተጠቀመችበት ነው ብሎ ለመናገር አያስደፍርም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አንዳንድ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች መታየት ጀምረዋል፡፡
በቅርቡ በሸራተን አዲስ አንድ መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዓድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ አመሰራረት፣ ራዕይና ተልዕኮ ላይ አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር በማሰብ ሀገር አቀፍ የምክክር ጉበኤ ተካሂዷል፡፡
በጉበኤው የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይቶች ተደርጎባቸዋል፡፡ ጥናታዊ ጽሁፎችን ካቀረቡት መካከል አዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት ዶክተር ሙሉጌታ ደበበ የዓድዋ ድል በኢትዮጵያ ከብሄራው ማንነት ግንባታ ጋር በተያያዘ ያበረከተውን ሚና የሚያብራራ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡ የዓድዋ ጦርነት እና ድል ኢትዮጵያ ነጻነቷን ጠብቃ እንድትኖር ከተጫወተው ሚና ጎን ለጎን በኢትዮጵያ ብሄራዊ ማንነት ግንባታ ላይ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ለዚህም የተለያዩ ማሳያዎችን አቅርበዋል፡፡
ከጦርነቱ ቀደም ብሎ በንጉሱ በታወጀው የክተት አዋጅ ከዳር እስከ ዳር ያለው ኢትዮጵያዊ ወጥቶ ረጅም ርቀት ተጉዞ እስከ አድዋ ሄዷል፡፡ በጉዞው ወቅት ኢትዮጵያውያኑ የተጓዙባቸው አካባቢዎች ያለው ህብረተሰብ ስንቅ በማቀበል፣ መንገድ በመምራት የበኩሉን ሚና ተጫውቷል፡፡ የቋንቋ እና የሃይማኖት ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው ጦርነቱ ኢትዮጵያዊነት እንዲጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ዶክተር ሙሉጌታ ማብራሪያ ከመላ ሀገራት ወደ ጦርነቱ የተመሙት ኢትዮጵያውያን በውጊያ ወቅት የከፈሉት መስዋዕትነት በራሱ የወንድማማችነት ስሜት የፈጠረ ነበር፡፡ በጦር ሜዳው ይሄ ከዚህ ብሄር ነው ሳይባባል በአንድነት ነበር ጠላቱን ይዋጋ የነበረው፡፡ የብሄር እና የሃይማኖት ልዩነት ሳያግደው የአንዱ ብሄር ወይም ሃይማኖት ተከታይ የሌላውን ብሄር ወይም ሃይማኖት ተከታይ ቁስለኛ የረዳበት የጦር ሜዳም ነው፡፡ እንደዚህ አይነት መስዋዕትነት በተከፈለበት የጦር ሜዳ ላይ አብሮ የተሰለፈ ህዝብ በውጊያው ማግስት ውስጡ የሚሰርጸው ወንድማማችነት ሃያል ነው፡፡ በመሆኑም ከየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ ወደ ዓድዋ የዘመተውን እንደ ወንድሙ እንዲመለከት ያደረገ ነበር፡፡
ከዓድዋ ድል በኋላም እያንዳንዱ ኢትዮጵያያዊ ወደ አካባቢው ሲመለስ ከጦርነት ለሚመለሱት ስንቅ በማቀበል፣ የታመመውን፣ የተጎዳውን እና የቆሰለውን በማከም እና በመጠገን ወደ ሀገሩ እንዲመለስ ያደረገበት አኳኋን የአንድነትን መንፈስ መፍጠሩን ነው ዶክተር ሙሉጌታ የተናገሩት፡፡
ይህ ማለት ግን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ማንነት ግንባታ በአድዋ ድል ተጠናቋል ማለት አይደለም የሚሉት ዶክተር ሙሉጌታ ይህ ማንነት በየጊዜው እየተገነባ የሚሄድ መሆኑንም እንዲሁ ያብራራሉ፡፡ ስለሆነም የዓድዋ ፓን አፍሪካን ዩኒቨርሲቲ መመስረት የተጀመረውን ብሄራዊ ማንነት ግንባታ ለማስረጽ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ በዩኒቨርሲቲው በዋናነት ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ማንነት ግንባታ የሚረዱ ጥናቶች እና ምርምሮች እንደሚካሄዱ እንዲሁም በዚህ ላይ የሚያተኩሩ ትምህርቶች እንደሚሰጡበት ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ሙሉጌታ እንዳብራሩት ይህ ማለት ግን ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ማንነት ግንባታ ሲባል የብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ማንነት ይቀራል ማለት አይደለም፡፡ ይልቁኑ በዚህ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ስራዎች ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ከራሳቸው ማንነት በላይ ኢትዮጵያዊ ማንነትን እንዲጎናጸፉ፤ በኢትዮጵያዊነት እንዲኮሩ፤ እንዲሁ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አድርገው እንዲያውለበልቡ የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
እንደ ሀገር ለመቀጠል በሀገር ላይ በሚመጣ ማንኛውም ጠላት የማይደራደር እና ኢትዮጵያ የኔ ናት የሚል ህዝብ መፍጠር ያስፈልጋል የሚሉት ምሁሩ ይህ ግን ብሄርተኝነት በጦዘበት በዚህ ወቅት በጣም አስቸጋሪ ነው ይላሉ፡፡ ሆኖም ዓለም የደረሰበት ነባራዊ ሁኔታ ይህን የሚያስገድድ ነው፡፡ ከብሄር ማንነት በላይ ኢትዮጵያዊ ማንነትን መደረብ የግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል የሚሉት ምሁሩ ይህ በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ በይሆንም ዩኒቨርሲቲው ለዚህ የራሱን ሚና ይወጣል ብለዋል፡፡
የዓድዋ ድል አፍሪካን ለመውረር የመጣ አውሮፓዊ ሃይል ለመጀመሪያ ጊዜ የተሸነፈበት እንደመሆኑ ለአፍሪካውያን ወንድማማችነትም መሰረት የፈጠረ ነበር፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካውያን ብሎም የመላው የዓለም ጥቁር ህዝቦች ድል ነው ያሉት ዶክተር ሙሉጌታ በዓድዋ ፓን አፍሪካን ዩኒቨርሲቲም ከመላው ኢትዮጵያ ብሎም ከመላው አፍሪካ የሚመጡ ተማሪዎች የመማር እድል ይሰጣቸዋል፡፡
ዶክተር ሙሉጌታ ዩኒቨርሲቲው አፍሪካውያንን ለማቀራረብም የላቀ ጠቃሜታ እንዳለው ነው የሚያነሱት፡፡ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ከሚማሩት መካከል 30 በመቶው ኢትዮጵያውያን ቢሆኑ እና 70 በመቶው ከተለያዩ አፍሪካ ሀገራት ለሚመጡ እድል ቢሰጣቸው ከፍተኛ መተሳሰርን መፍጠር ይቻላል፡፡ እነዚያ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው ወቅት ጥብቅ ትስስር ፈጥረው ወደ ሀገራቸው ቢመለሱ አፍሪካውያንን ለማስተሳሰር ለሚደረገው ጥረት አጋዥ ይሆናል፡፡
ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ተማሪዎች በአካል መገናኘታቸው እና እርስ በርስ መማማራቸው ከሚፈጥረው ወንድማማችነት ባሻገር በአሁኑ ወቅት በዓመት በጣት የሚቆጠሩ ጊዜያት ብቻ የሀገራቱ መሪዎች በአፍሪካ ህብረት የሚያደርጉትን ግንኙነት ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ተማሪዎች በየቀኑ እንዲገናኙ እድል ይፈጥራል፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ደግሞ በቀጣይ በየሀገራቸው የመሪነት ቦታ የመያዝ ዕድላቸው ሰፊ በመሆኑ ለአህጉሪቱ ትስስር የራሱ ሚና አለው፡፡ የዩኒቨርሲቲው አንዱ ዓላማ ስለ አፍሪካውያን ጥናቶችና ምርምሮችን ማካሄድ እንደመሆኑ እነዚህ ትምህርቶች እና ምርምሮች የአህጉሪቱን እና የህዝቦቿን ትስስር እንደሚያጠናክርም ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ የዩኒቨርሲቲው ግንባታ ዝግጅት የደረሰበት ደረጃን የሚያመላክት ሪፖርት በዩኒቨርሲቲው አስተባባሪ ኮሚቴ የቀረበ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው የማስተር ፕላን መነሻ ዲዛይንም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ የዩኒቨርሲቲው አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ቢተው በላይ የዩኒቨርሲቲው ግንባታ ኮሚቴ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ያከናወናቸውን ተግባራት ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና በኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩወሪ ሙሴቬኒ የመሰረት ድንጋይ መቀመጡን ነው ያብራሩት አቶ ቢተው የትግራይ ክልላዊ መንግስት ማዕከላዊ ዞን፣ ከአድዋ ወረዳ እና ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ከ150 ሄክታር በላይ መሬት ከልለው ማስረከባቸውን ነው ያብራሩት፡፡
የዩኒቨርሲቲውን ግንባታ ለማስጀመር ከአድዋ ወረዳ እና ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር ከአካባቢው ለሚነሱ ነዋሪዎች የካሳ ክፍያ ጥናት የሚያካሂድ ኮሚቴ ተዋቅሮ ጥናቱን የጀመረ ሲሆን ይኸውም ጥናት በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ነው የገለጹት፡፡
እንደ አቶ ቢተው ማብራሪያ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም አቅራቢነት ዩኒቨርሲቲው በአፍሪካ ህብረት እውቅና ማግኘቱም ትልቅ ስኬት መሆኑን ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲው ምስረታ ጽንሰ ሃሳብና ረቂቂ ቻርተር ተዘጋጅቷል፡፡
ኮሚቴውን ለማጠናከር በማሰብ ከውጭ ጉዳይ፣ ከባህልና ቱሪዝም፣ ከትምህርት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተውጣጣ ተጨማሪ ኮሚቴ እንዲቋቋም መደረጉን ነው ያብራሩት፡፡ ኮሚቴውም ከአስተባባሪ ኮሚቴ ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡ የአስተባባሪ ኮሚቴውን ህጋዊነት የማረጋገጥ እና የማደራጀት ተግባራት መከናወናቸውንም ነው ያብራሩት፡፡
የዩኒቨርሲቲው የማስተር ፕላን መነሻ ዲዛይን በበርካታ ኢትዮጵያውያን ኢንጂነሮች በነጻ የተዘጋጀ ሲሆን ባለሙያዎች በነጻ የተሰራውን የመነሻ ማስተር ፕላን ዲዛይን አርክቴክት ፕሮፌሰር ፋሲል ጊዮርጊስ ለጉባኤው ታዳሚዎች ገለጻ አድርገዋል፡፡
ከአድዋ ከተማ በስተደቡብ ምስራቅ ወደ አቢ አዲ በሚወስደው መንገድ አጠገብ ለሚሰራው የዓድዋ ፓን አፍሪካን ዩኒቨርሲቲ የተመረጠው ቦታም ለእይታ አመቺ እና በርካታ ሳቢ የተፈጥሮ አቀማመጥ ያለው ሲሆን፤ የአድዋ ከተማን በግልጽ ሊያሳይ በሚችል መልኩ መቀመጡን ነው የተናገሩት፡፡
ከክልሉ መንግስት የተሰጠው መሬት ላይ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሰራውን ቶፖግራፊክ ማፕ ከግምት በማስገባት የማስተር ፕላን ዲዛይኑ ተዘጋጅቷል፡፡ ፕሮጀክቱ ሰፊ በመሆኑ ደረጃ በደረጃ የሚሰራ ነው፡፡ ከመጀመሪያ ጀምሮ እንዴት እያደገ እንደሚሄድም በዲዛይኑ ላይ አመላክተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲውን ከዓድዋ ከተማ ጋር ለማስተሳሰር መታቀዱን ያነሱት ፕሮፌሰር እንዴት የአካባቢው መንገዶች ከዩኒቨርሲቲው ጋር እንዴት ይተሳሰራሉ የሚለው በማስተር ፕላኑ ላይ ተመላክቷል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የሚገነባበት ቦታ ተዳፋት በመሆኑ በአንድ በኩል እድል ሲሆን በሌላ በኩል ተግዳሮት ነው ያሉት ፕሮፌሰር ፋሲል በዚህ ተዳፋት ቦታ ላይ ህንጻዎቹን እንዴት ማስቀመጥ እንደሚቻልም በገለጻቸው ዳሰዋል፡፡
እንደ አርክቴክት ፋሲል ገለጻ በማስተር ፕላኑ መነሻ ዲዛይን ላይ የሚገነቡ ህንጻዎች የአፍሪካውያንን ባህል እና ከኢትዮጵያውያን ብሄር ብሄረሰቦች ባህሎች መካከል ጠቃሽ እና ዋና ዋና የሚባሉትን መያዝ እንዳለበት ተመልክቷል፡፡
የአድዋ ጦርነት መላው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ከአራቱም አቅጣጫዎች በህብረት ተነስተው የውጭ ወራሪን የታገሉበት ስለሆነ የህንጻዎቹ አቀማመጥ ያንን ጽንሰ ሀሳብ እንዲያንጸባርቅ እንደሚደረግ ነው ያብራሩት፡፡
በዩኒቨርሲቲው ጊቢ ውስጥ ከፍታ ቦታ ላይ ትልቅ ሀውልት ይሰራል፡፡ ሀውልቱ ከውጭ የሚታይ እና የዩኒቨርሲቲው አርማ እና የኢትዮጵያ እና የመላ አፍሪካውያን ብሎም የመላውን ጥቁር ህዝቦችን ትግል የሚያሳይ እንደሚሆንም ነው የተናገሩት፡፡
ፕሮፌሰር ፋሲል እንዳብራሩት ወደ ዩኒቨርሲቲው መግቢያ ሶስት ዋና ዋና በሮች እና አንድ ተጨማሪ መግቢያ በር ይኖረዋል ያሉት አርክቴክቱ በመግቢያ አካባቢ የኢትዮጵያውያንን እና የአፍሪካውያንን አኗኗር የሚያንጻባርቁ ስዕሎች እና ቅርጻ ቅርጾች ይኖራሉ፡፡
በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ጊቢ ውስጥ አደባባዮች ይኖራሉ፡፡ አደባባዮቹ በጥቁር ህዝቦች በነጻነት ትግል ውስጥ ከፍተኛ ቦታ በተሰጣቸው ቦታዎች ስም የሚሰየሙ ይሆናሉ፣ ለአብነት ያህል ስዌቶ አደባባይ፣ አድዋ አደባባይ የሚሉ ስያሜዎች እንደሚሰጣቸው ነው የተናገሩት፡፡
ዩኒቨርሲቲው የመማሪያ፣ የተማሪዎች ማደሪያ እንዲሁም የስታፍ ማደሪያ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፤ ባህላዊ ኤግዝቢሺኖች የሚታይበት፣ ኮንፍረንስ የሚካሄድበት እና የህትመት ስራዎች በተለይም በዓድዋ ጦርነት ዙሪያ የተሰሩ ጥናቶች የሚታዩበት ከከተማው ጋር ቀረቤታ ያለው የባህል ማዕከል ይኖረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያው ዙር 2 ሺ ተማሪዎችን ይቀበላል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከከተማው እና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ትስስር እንዲኖረው ይፈለጋል፡፡ ጎብኚዎች መጥተው ከጥናት፣ ከባህል እና ከኤግዚቢሽን ጋር ግንኙነት እንዲኖራቸው ይደረጋል፡፡
የህንጻዎቹ አሰራር የመላውን አፍሪካውያን ባህላዊ ቤት አሰራሮችን እና መንደሮች በሚያንጸባርቅ መልኩ ይገነባል ነው ያሉት፡፡ ህንጻዎችም በተለያዩ ፓን አፍሪካን አቀንቃኞች፣ ምሁራን እና ጀግኖች ስም ይሰየማሉ፡፡
ፕሮፌሰሩ እንዳብራሩት ከሆነ ህንጻዎቹ በሚሰሩበት ወቅት የአካባቢውን ተፈጥሮ መልክ እንዲይዙ ጥረት ይደረጋል፡፡ የህንጻዎቹ ቀለምም አካባቢውን የማይጫኑ እና የአካባቢውን ቁሶች የሚጠቀሙ በተቻለ መጠን ዘላቂ ዲዛይን የሚባለውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ የተከተሉ ይሆናሉ፡፡ በአጠቃላይ ህንጻዎቹ ከተፈጥሮ ጋር ከፍተኛ ትስስር እንዲኖራቸው ትኩረት ይደረጋል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደተናገሩት የዓድዋ ድል ዘመን ተሻጋሪ ገድል ተነግረው የማያልቁ በርካታ ቁም ነገሮችን ይዟል፡፡ የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያውያን አልፎ የመላ የጥቁር ህዝቦች የአርነት ትግል ምሳሌ ብሎም የኩራት ምንጭ ነው፡፡
‹‹የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ልጆች ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር ሃያልነት ፣ የሰላምን ውድ ዋጋ፣ የጭቆና አገዛዝን አስከፊነት ጠንቅቀን ለምናውቅ ለኛ ለኢትዮጵያውያን ከአንድ የጦር አውድማ ድልም በላይ ነው›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ታሪክ በኩራት ሰርክ እንደሚተርከው ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ለአፍታም ቢሆን ለድርድር እንደማያቀርቡ አብራርተዋል፡፡
በመላው ዓለም የሚገኙ ታላላቅ የትምህርት እና ምርምር ተቋማት ስለ ዓድዋ ጦርነት ብሎም ድሉ በጥቁር ህዝቦች ፀረ ቀኝ ግዛትና ፀረ ጭቆና ታሪክ ውስጥ ስላበረከተው ጉልህ አስተዋጽኦ በርካታ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ሰርተዋል፡፡ ‹‹የታሪኩ ባለቤት የሆንን እኛ ግን የድሉን ዕለት ከመዘከር ያለፈ ይህ ነው የሚባል ሥራ ሰርተናል ለማለት አያስደፍርም›› ብለዋል፡፡
ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ ጦርነቱ በተካሄደበት ሥፍራ ላይ ዩኒቨርሲቲ በማነጽ ስለ ዓድዋ ታሪክ ጥቅል ምርምሮች እንዲካሄዱ አልፎም ዩኒቨርሲቲው የጥቁር ህዝቦች ጥናት የልህቀት ማዕከል በመሆን እንዲያገለግል ለማስቻል ጉዳዩ ያገባናል ያሉ ዜጐች በመሰባሰብ ጥረቶችን በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ገልጻ ዩኒቨርሲቲው ብሔራዊ መግባባትን ከማጠናከር አልፎ የአፍሪካውያንን ብሎም የጥቁር ህዝቦችን ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል፡፡ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ይህ ኃላፊነት አለብን፤ ኃላፊነታችንንም መወጣት ይጠበቅብናል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የመንግስት ሳይሆን የህዝቦች እና የነጻነት ወዳዶች ሁሉ ነው፡፡ ከኢትዮጵያም አልፎ የአፍሪካውያን ዩኒቨርሲቲ ነው እንዲሁም በመላ ዓለም ለነጻነት የታገሉ የነጻነት ታጋዮች ዩኒቨርሲቲ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግስት አድርጎ መመልከት ስህተት ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን የዩኒቨርሲቲውን ስራ ለማስጀመር የፌዴራል መንግስት 200 ሚሊዮን ብር መመደቡን ለጉባኤው ይፋ አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም መላ የሀገሪቱ ህዝቦች አንፀባራቂ ታሪካቸውን ለሚዘክረው ለዚህ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ በፍጥነት መከናወን የራሳቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ የጉባኤው ታዳሚዎችም ወደ መጡባቸው አካባቢዎች ሲመለሱ ለዩኒቨርሲቲው እውን መሆን አስፈላጊ የሆነውን የዜጎች ተሳትፎ በማስተባበር ግንባር ቀደም ሚና መጫወት አለባቸው፡፡
የሁሉም ክልል መስተዳድር አካላትም ለዚህ በዜጎች ግንባር ቀደም ጠንሳሽነትና መሪነት ለሚቋቋመው ዩኒቨርሲቲ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ከአደራ ጭምር አሳስበዋል፡፡
የፌዴራል መንግስት እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ለዚህ እና ሌሎች መሰል ብሔራዊ መግባባትን ለሚያጠናክሩ የልማት ፕሮጀክቶች የሚያደርገውን ድጋፍ በተጠናከረ መንገድ የሚያስቀጥል ይሆናል፡፡ ይህ ዩኒቨርሲቲም ግንባታው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ በተመረጡ የትምህርት ዘርፎች ተማሪዎችን ከአገር ውስጥም ሆነ ከመላ አፍሪካ ተቀብሎ የመማር ማስተማር እንዲሁም የምርምር ሥራዎችን እንዲያካሂድ መንግስት ያልተቋረጠ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡
ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እንዲሁም ተራማጅ የህዝብ ትግል ደጋፊዎች ለዩኒቨርሲቲው ግንባታ ድጋፍ እንዲያደርጉ ሰፊ የዲፕሎማሲ ስራዎች በትጋት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው መመስረት ብቻውን በቂ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የዓድዋ ድል ከዩኒቨርሲቲም በላይ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በመሆኑም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሃላፊነት ወስዶ የዓድዋ ድል ሊሰጠን የሚችለውን ትሩፋት በሙሉ አሟጠን እንድንጠቀም ጥናት እንዲያካሂድ በመንግስት የቤት ስራ መሰጠቱን ነው የተናገሩት፡፡
ጦርነቱ የተካሄደባቸው የእነዚያ የዓድዋ ተራሮች መንገዶች እና የገድል ስፍራዎች በሙሉ ሊጠበቁ እና ለቱሪስትም ምቹ ሆነው ሊጎበኙ የሚገቡ ናቸው፡፡ መላውን የዓድዋ ተራራ ዙሪያ እና ጦርነቱ የተካሄደበትን ስፍራ በሙሉ የሚገልጽ ሰፊ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡
በጉባኤው የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ ኡጋዞችና ሱልጣኖች፣ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ምሁራንና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡
ለሁለት ቀናት በቆየው በዚህ ጉበኤ ላይ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን ጥናታዊ ጽሁፎችን አቅርበዋል፡፡ ከቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፎች መካከል የዓድዋ ጦርነት ዋዜማ፣ የዓድዋ ድል ለአፍሪካውያን ተምሳሌቱ፣ ዓድዋ ድል በኢትዮጵያ ሀገር ግንባታ የተጫወተው ሚና እና የዓድዋ ታሪክ አስተማሪነቱ በሚሉ ርዕሶች የቀረቡ ጽሁፎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

መላኩ ኤሮሴ

Published in ፖለቲካ


የአካባቢና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት በ2009 በጀት ዓመት በደን ልማት ዘርፍ ያገኛቸውን የምርምር ውጤቶች የማስተዋወቂያ የሁለት ቀን አውደጥናት ሰሞኑን በቢሾፍቱ ከተማ አካሂዶ ነበር፡፡ አውደ ጥናቱ በዋናነት የምርምር ውጤቶች ከመደርደሪያ ላይ ወርደው ለአገር ኢኮኖሚ ፋይዳ ያመጡ ዘንዳ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን ለማንሸራሸር ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡ ዶክተር ተፈራ መንግስቱ በአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር የደን ሴክተር አቅም ግባታ ፕሮግራም አስተባባሪ ናቸው፡፡ በአውደ ጥናቱ ላይ የምርምር ውጤቶችን ከተጠቃሚው ጋር እንዴት ማስተሳሰር እንደሚቻል የሚያስገነዝብ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡
በፅሁፉቸውም በዋናነት የምርምር ውጤቶችን ለተጠቃሚ ለማድረስ አገሪቱ በአሁኑ ወቅት የምትከተላቸው መንገዶች ኋላቀርና በቴክኖሎጂ ያልተደገፉ መሆናቸውን ያመለክታሉ፡፡ የአገሪቱ የደን ልማት ስራ በእስከዛሬው አካሄድ በአብዛኛው ከችግር ማውጣት የሚያስችል አይደለም፡፡ በተለይም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና ለኢኮኖሚው እምረታዊ ለውጥ ለማምጣት እገዛ አላደረገም፡፡ ይህም ደግሞ ተመራማሪዎችም ሆነ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የቤት ስራቸውን በሚገባ ካለመወጣታቸው ጋር ተያይዞ የሚመነጭ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በተለይም የደን ኤክስቴንሽን ስራዎች እየተከናወኑ ያሉት በአንድ ወቅት ዘመቻ መልክ በመሆኑ ቀጣይነት ያለው ለውጥ ማምጣት አለመቻሉን ነው የሚጠቅሱት፡፡
የተሰሩ የምርምር ውጤቶች ወደተጠቃሚ ያለመድረሳቸውና መደርደሪያ ላይ ለመቅረታቸው ዋነኛ ምክንያት የሚሉትም ዘርፉን ለመደገፍ የሚያስችል የኢንቨስትመንት ስራ አለመሰራቱ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ «በደን ልማት ትርፍ ለማግኘት አመታት መጠበቅ የግድ የሚል በመሆኑ ባለሃብቱ ወደዚህ ዘርፍ ለመግባት አይሻም፤ በዚህ ረገድ የተሰራው የማስተዋወቅ ስራም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም» ይላሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ «የደን ልማት ስራ አመቱን ሙሉ ሊከናወን የሚገባ ነው» በማለት የሚናገሩት አስተባባሪው፤ የኤክስቴንሽኑን ስራ አመቱን ሙሉ ማከናወን ይቻል ዘንድም በዋናነት ለእዚያ የሚመጥን ባለሙያ የማፍራቱ ስራ ብዙም ትኩረት አለመሰጠቱን ያመለክታሉ፡፡ የሚገኙ የምርምር ውጤቶች ለተጠቃሚ ተደራሽ ማድረግ ያልተቻለውም በሚፈለገው ልክ ባለሙያ ባለመኖሩ እንደሆነም ይጠቅሳሉ፡፡
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ አገሪቱ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ነድፋ የአካበቢ ጥበቃና የተፋስስ ልማት ስራዎች ማከናወን ከጀመረች አመታት ቢቆጠሩም የሚሰራው ስራ እውቀት ላይ የተመረኮዘ አይደለም፡፡ በአየመቱ የሚተከሉ ዛፎችን ቁጥር ከማብዛት ባለፈ አመቱን ሙሉ ተንከባክቦ በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲኖራቸው ማድረግ እምብዛም ትኩረት አልተሰጠውም፡፡
«ኢትዮጵያ የደን ሃብቷ ለኢኮኖሚዋ የላቀ ሚና እንዲጫወት በማድረግ ረገድ ከሌሎች ጎረቤት አገሮች በተሻለ ምቹ ሁኔታዎች አሏት» የሚሉት ዶክተር ተፈራ በተለይም ደግሞ ተለይነት ያለው ስነምህዳሯና የአየርንብረቷን በመጠቀም እንዲሁም የስነ ህይወት ጥበቃን በማሻሻል ሃብቱን ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል ይጠቁማሉ፡፡ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸውን ዝርያዎች ለይቶ በእነርሱ ላይ ሰፋ ያለ ምርምር መካሄድ አለበት፡፡ ይህም ደግሞ ለተለያዩ ልማቶች ከውጭ የሚመጡትን የጣውላ ምርቶች በማስቀረት የውጭ ምንዛሬ ለመታደግ ያግዛል ባይ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ የአካባቢና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት የማህበራዊ ኢኮኖሚና የምርምር ኤክስቴንሽን ዳይሬክተር ዶክተር አለማየሁ ነጋሳ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ ባለፉት ሁለት አመታት ኢንስቲትዩቱ ከተሰጠው ተልዕኮ አንፃር የደን ሃብት በተጨባጭ ለኢኮኖሚ እድገት ድጋፍ ማድረግ የሚያስችሉ በርካታ የምርምር ስራዎችን አውጥቷል፡፡ በተለይም በአውደ ጥናቱ ይፋ የተደረጉት ሶስት የመሬት አጠቃቀም ስልቶችን የሚጠቁሙ ጥናቶች ወደ መሬት ማውረድ ከተቻለ እመርታዊ የሚባል ለውጥ ማምጣት ያስችላሉ፡፡
«በአገራችን የመሬት አጠቃቀም በከፍተኛ ሁኔታ እየተለወጠ ነው ያለው» የሚሉት፤ ዳይሬክተሩ፤ በዋናነትም ደግሞ ደንና ከቁጥቋጦ ጋር የተያያዙት መሬቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየተራቆቱና ወደ ሰፋፊ እርሻነት እየተለወጡ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡ ይህም ደግሞ በአየር ንብረት ለውጡ እያበረከቱት ያሉት አሉታዊ ተፅዕኖ በግልፅ እየታየ መምጣቱን ያመለክታሉ፡፡ ለአብነትም በአሁኑ ወቅት በጋምቤላ፥ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በምዕራብ ኦሮሚያ በቆላማና ደረቃማ አካባቢዎች ያሉት የቁጥቋጦ ዛፎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተመናመኑ መሆኑን በመጥቀስ፡፡ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉትም የእጣን ዛፎች አደጋ ላይ የወደቁበት ሁኔታ መኖሩንም ነው የሚጠቁሙት፡፡
በዚህ ረገድም ኢንስቲትዩቱ ያወጣቸው የምርምር ሶስት ውጤቶች የግብርና የደን ልማት ስራዎችን ጎን ለጎን በማካሄድ ችግሩን ከመቅረፍ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የሚያመጡ ናቸው፡፡ በዋናነት በጣም ፈጣን እድገት ያላቸው የዛፍ አይነቶችንም በመትከል ለውጤት ከበቁ በተለይ በ15 ዓመት ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ጥናቶቹ አመላክተዋል፡፡ «በእርግጥ ወደ መጀመሪያ አካባቢ ከፍተኛ የሆነ መዋዕለ ንዋይ የሚፈልግና ትርፍ የሚገኘው በረጅም ጊዜ ርቀት በመሆኑ ኢንቨስተሮች ብዙውን ጊዜ ለመግባት አይደፍሩም፤ ይሁንና ባካሄድነው የምርምር ስራ የሚያስፈልገውን ሁሉ ዋጋ ተከፍሎ እነዚህን ዛፎች ማልማት ከተቻለ በ15 ዓመት ጊዜ ውስጥ 32 እጥፍ ትርፍ ማግኘት እንደሚችሉ ጥናታችን ያሳያል» በማለት ያስረዳሉ፡፡
በምርምር የተገኙ ውጤቶችን ለተጠቃሚው ማድረስ ያስችል ዘንድ በተለይም እርሳቸው የሚመሩት የስራ ክፍል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ይናገራሉ፡፡ በተጨማሪም በተጨባጭ አርሶአደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ምርምሮች ለፖሊሲ ግብዓት ይሆኑ ዘንድ በህትመት መልክ ተዘጋጅተዋል፡፡ «ይህም ለውሳኔ ሰጪ አካላት አቅጣጫ የሚጠቁም ከመሆኑም ባሻገር የተለያዩ የመሬት አጠቃቀሞችን በመከተል ሊገኝ የሚችለውን ጥቅም ግንዛቤው እንዲኖረው ያደርጋል» ይላሉ፡፡
የምርምር ውጤቶችን አባዝቶ ወደ ተጠቃሚው የማድረሱ ስራ ምንም እንኳ የሌሎች ባለድርሻ አካላት ሚና ቢሆንም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በተወሰነ መጠን ለአርሶአደሩ የማስተዋወቅ ስራ በኢንስቲትዩቱ መከናወኑን ይጠቁማሉ፡፡ ለአብነት ያህልም የእጣን ዛፍን ሳይቆርጡና ሳይነቅሉ የማባዛት ቴክኖሎጂ ማለትም ዛፉን በማድማት ብቻ ማከናወን የሚያስችል ምርምር በተለያዩ እጣን አብቃይ አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶአደሮች ማስተዋወቅ መቻሉን በመጥቀስ፡፡
በተጨማሪም ኢንስቲትዩቱ የኤሌክትሮኒከስ እቃዎች ተረፈ ምርት በአካባቢ ብክለት ላይ እያበረከቱ ያሉትን አሉታዊ ተፅእኖ የሚያሳይና ሊደረግ የሚገባውን የመፍትሄ ሃሳብ የሚጠቁም ጥናት አከናውኗል፡፡ በዋናነትም በናሙና መልክ በተወሰዱ አካባቢዎች የኤሌክትሮኒክስ ተረፈ ምርቶች አወጋገድ ስርዓት ያልተበጀለት በመሆኑ በሰዎች ጤና ላይ እያደረሱ ያሉትን ጉዳት በዝርዝር ለማሳየት መቻሉን ይጠቅሳሉ፡፡ በምርምሩ እነዚህን ምርቶች በምን መልኩ በማስወገድ ብክለቱን ማስቆምና የአየር ንብረት ለውጡን መቀነስ እንደሚቻል ጠቋሚ ሃሳቦች በህትመት መልክ መዘጋጀታቸውን ተናገረው ይህም ለፖሊሲ አውጪ አካላት ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን ነው ያስረዱት፡፡
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አጌና አንጁሎ ደግሞ ኢንስቲትዩቱ በአዋጅ ከተቋቋመ ሶስት አመት ቢሆነውም በይፋ ስራ ከጀመረ ገና ሁለት አመት መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ስራ ሲጀምርም በአዲስ አበባ ከነበሩት ሁለት ነባር የምርምር ማዕከላት ባሻገር በጅማ፥ በሃዋሳ፥ በድሬዳዋ መቀሌና ባህርዳር ተጨማሪ ማዕከላትን ማቋቋሙን ያመለክታሉ፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በጥቅሉ 88 የምርምር ፕሮጀክቶች በመቅረፅ ወደ ስራ መግባቱንና 260 የሚሆኑ የምርምር ስራዎች ማከናወኑን ያስረዳሉ፡፡
ከዚህ ውስጥም በመካከለኛ ደረጃ 42 መረጃና ቴክኖሎጂዎች ማውጣት የተቻለ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ለባለድርሻ አካላት በማስተዋወቅና በማስተቸት ለህብረተሰቡ ጥቅም ሊሰጡ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡ በተለይም የምርምር ውጤቶቹ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ መደርደሪያ ላይ እንዳይቀሩና ወደ ተጠቃሚዎቹ እንዲደርሱ የአሰራር ስርዓቶችን መዘርጋቱን ይጠቁማሉ፡፡ ቴክኖሎጂዎቹ መሬት ላይ ወርደው ውጤት ያመጡ ዘንድ ፖሊሲ አውጪዎች ግንባር ቀደም ሚናቸውን እንዲወጡ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ቃሬ ጨዊቻ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በ2017 ዓም መካከለኛ ኢኮኖሚ ካላቸው ተርታ አገራት ለመሰለፍ በሁሉም መስኮች ከፍተኛ ጥረትና ርብርብ እያደረገች ነው፡፡ የሚያጋጥሙ ልዩ ልዩ ተግዳሮቶችን በመቋቋም ለአገሪቱ ልማትና እድገት የሚያፋጥኑ ፕሮግራሞች ተግባራዊ ሆነዋል፡፡ በተለይም አገሪቱ በአካባቢ በደንና በአየር ንብረት ለውጥ እያጋጠማት ያሉትንና ወደፊትም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ ለመፍታት ኢንስቲትዩቱ ተቋቁሞ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡
«ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመ ሶስት አመታት ብቻ ቢሆንም የተጣለበትን ተልዕኮ ለመወጣትና አገራዊ ራዕዩን ዕውን ለማድረግ እያከናወነ ያለው ጅምር ስራ የሚበረታታ ነው» ይላሉ፡፡ በዋናነትም በአካባቢ በደንና በአየር ንብረት ለውጥ ዘርፍ ችግር ፈቺ የሆኑ የምርምር ስራዎችን በማውጣት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር ከምታደርገው ጥረት ጎን ለጎን ከኢንዱስትሪዎች መስፋፋትና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን አሉታዊ ተፅእኖ ለመቀነስ ምርምሩን የማጠናከር ስራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡
በሰውና በአካባቢ ጤንነት ላይ የማይቀለበስ ጉዳት ሳያደርስ ልማቱ ዘላቂነት ባለው መልኩ እንዲቀጥል ኢንስቲትዩቱ በአካባቢ ብክለት አያያዝ ዘርፍ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ የምርምር ስራዎችን በስፋት ማከናወን እንደሚገባውም ሚኒስትር ዴኤታው ያስገነዝባሉ፡፡ « ከምርምር የሚገኙ ውጤቶች ለጊዜያዊና ዘላቂ ችግሮች መፍትሄ የሚጠቁሙ ከመሆናቸውም በላይ ዜጎችን በምቹ አካባቢ እንዲኖሩ ያስችሏቸዋል» ብለው የአካባቢ ልማትን ለማረጋገጥ የተቋቋመው ቤተ ሙከራ ከሚጠበቅበት አኳያ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅበት ነው የተናገሩት፡፡
እንደ አቶ ቃሬ ማብራሪያ፤ በደን ሃብቱ ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስና ሽፋኑን ለመጨመር እንዲሁም የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ ለማድረግ አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን ጥቅም ለማሳደግ የሚቻለው በምርምር የሚገኙ ውጤቶችን መጠቀም ሲቻል ነው፡፡ ይህንንም በመገንዘብ የምርምር ተቋሙ በደን ዘርፍ የተለያዩ የምርምር ፕሮጀክቶችን እየቀረፀ ከባለድርሻ አካላት የሚያገኛቸውን ግብአቶች እያካተተ ተግባራዊ በማድረግ ለዘርፉ ልማት የበኩሉን ሚና መጫወት ይገባዋል፡፡
«ከጥናቶቹ ፋይዳ አንዱና ዋነኛው አገራችን ደኖችን በማስፋፋት ከምታገኘው ጥቅም ባሻገር በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ሊመጣ የሚችለውን ጉዳት አስቀድሞ ለመተንበይ፤ በዚህም ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስና ጥንቃቄ እንዲደረግ የመፍትሄ ሃሳብ ለሚመለከታቸው አካላት ማቅረብ ነው» ይላሉ፡፡ በመሆኑም የምርምር ኢንስቲትዩቱ በአካባቢ በደንና በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ አገሪቱ የምትፈልጋቸው ሳይንሳዊ መረጃዎችና ቴክኖሎጂዎችን ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረትና ርብርብ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በምርምሩ የተገኙ ውጤቶች በባለድርሻ አካላት እንዲዳበሩ ተሳትፏቸውን ሊያሳድጉ ይገባልም ባይ ናቸው፡፡

 ማህሌት አብዱል

Published in ኢኮኖሚ
Thursday, 01 February 2018 17:51

የገበያው ሴራ እስከየት?

ሀገራዊ ገበያው ምንም አይነት የሸቀጥና የአቅርቦት እጥረት ሳይኖርበት ሆን ተብሎ በሚሰራ የኢኮኖሚ አሻጥርና ደባ ሕዝቡን ለማማረርና ለማስከፋት ቢሮክራሲውና ስግብግብ ነጋዴው በመመሳጠር እየሰራ ይገኛል፡፡ ግልጽ አላማው ሕብረተሰቡ በሥርዓቱ ላይ እንዲማረር ለማድረግ ሆን ተብሎ ታቅዶ እየተሰራ ያለ እኩይ ስራ ነው፡፡ በሀገራችን ገበያ ላይ የስኳር የዘይት እንዲሁም የሌሎች መሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት እጥረት የለም፡፡ እየተፈጠረ ያለው ችግር በቢሮክራሲው መነሻነት የሚታየው ሰው ሰራሽ ችግር ሲሆን ይህን በማባባስ ረገድ ደግሞ ቁልፍ ሚና የሚጫወተው ተባባሪ ነጋዴው ነው፡፡ ያለምንም መነሻ ምክንያት በሕዝቡ ላይ የመልካም አስተዳደር ችግር የሚፈጥሩት አካላት የሚሰሩት ስራ ውጤት ነው፡፡
በግርግር ለመክበር የሚደረገው የነጋዴው መክለፍለፍ አጋጣሚዎችን በመጠቀም ሁከትና ግርግር ለሌባ ያመቻል ይሉት አይነት የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር ትራንስፖርት የለም ሸቀጦች እንደልብ አይገቡም በሚል ሰበብ ሕብረተሰቡን እያስመረሩት ይገኛሉ፡፡ የተለያዩ ሸቀጦች ዋጋ ከጣሪያ በላይ እያወጡ ሕብረተሰቡን እንዲማረር ለማድረግ በነጋዴው በኩል የሚፈጸም ደባ ነው፡፡
የአንድ ሰሞን የሞቅ ሞቅ ስራ ካልሆነ በስተቀር ተገቢ በሆነ መልኩ መስመር የዘረጋ የቁጥጥርና ቋሚ የክትትል ሥርዓት ስለሌለ፤ ቢኖርም በአግባቡ ስላልሰራ በሕገወጥ መንገድ በሸቀጦች ላይ እንዳሻቸው የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ የሚፈነጩ ነጋዴዎች በዝተዋል፡፡ በሌሎች ሀገሮች ልምድና ተሞክሮ የገበያ እጥረት ሲፈጠር መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ ሊደረግ ይችላል፡፡ ገበያው ሲረጋጋ ደግሞ የተጨመረው ዋጋ ይወርዳል፡፡ተመልሶ የነበረበት ቦታ ይሆናል፡፡
በእኛ ሀገር ደግሞ የተለየ ኢኮኖሚክስ ነው ያለው፡፡ ነጋዴው በሰበብ አስባብ አንዴ ዋጋ ከተጨመረ ያንኑ ጠብቆ እየጨመረ ይሄዳል እንጂ ዋጋ አይቀንስም፡፡ ለሸማቹ የሚሰጠው መልስ ብትገዛ ግዛ ካልፈለክ ተወው የሚል ነው፡፡ በዚህ መሰረት ሕብረተሰቡ እጅግ ለከፋ ጉዳት ተጋልጦአል፡፡
ሕግና ሥርዓት ማስከበር ያለባቸው መንግስታዊ አካላት በአግባቡ ሊደርሱለት ከምዝበራና ከመገፈፍ ሊያድኑት ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ አልቻሉም፡፡ ጤፍና ጥራጥሬ፣ የምግብ እህሎች አትክልቶች በገፍና በከፍተኛ ደረጃ በሚመረትበት ሀገር ስግብግብ በሆነ የነጋዴ ፍላጎት የተነሳ ከሕግና ከሥርዓት ውጭ የገበያውን ዋጋ እያናሩ ሕዝብን ማስለቀስ የወንጀልም ወንጀል ነው፡፡
ጤፉ ጥራጥሬው ከአሜሪካ ወይንም ከእንግሊዝ ወይንም ከሌሎች ሀገራት የሚመጣ አይደለም፡፡ ጭርሱንም በርካሽ ዋጋ ለሕዝቡ መገኘት የነበረባቸው እነዚሁ የራሳችን የሆኑ ምርቶች ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያ የአርሶ አደሮች አርብቶ አደሮች ሀገር ናት፡፡ የሕዝቡ ቁጥር ይጨምር እንጂ ከድሮውም እጥፍ የበለጠ ምርት ነው የሚመረተው፡፡ የገበሬው ጎተራ ሙሉ ነው፡፡ ተርፎ ነው ለገበያ የሚወጣው፡፡ የቀንድ ከብቶችም ሞልተው የተረፉባት ሀገር ነች፡፡
እንዲህም ሆኖ ነጋዴው ከአርሶ አደሩና ከአርብቶ አደሩ በቀላል ዋጋ እየገዛ በሕዝቡ ላይ የኑሮ ውድነት በመፍጠር እየተጫወተ እየቀለደበት ይገኛል፡፡ አሳፋሪም አሳዛኝም ነው፡፡ የቱንም ያህል ነጻ ገበያ ነው ቢባልም ነጋዴው ሕግና ደንብን አክብሮ እንዲሸጥ የማድረግ ስራ በመሚመለከታቸው መንግስታዊ አካላት አልተሰራም፡፡ ከጀርባ መሞዳሞድና የእንካ በእንካ ጨዋታዎች አሉ፡፡ ነጋዴው የያዘውን ሸቀጥም ሆነ ምርት ለመሸጥ ሕዝብ ነው የገበያው ማእከል፡፡ እየተጫወተ ያለውም በሕዝቡ ነው፡፡
ድሮ ርካሽ ነበር የሚባለው የሕዝቡ ቁጥር መጠነኛ ስለሆነ ሊሆን ይችላል፡፡ ሀገሪቱ ከድሮውም በበለጠ ምርት እየሰጠች ባለችበት ሰአት ሁሉን ነገር ማስወደድ ጤነኛ ነገር አይደለም፡፡ አደጋም አለው፡፡ አንዱ አማራጭ ለሕዝቡ ገበያ ላይ የሚቀርቡትን ሸቀጦች ሙሉ በሙሉ በሕዝብ አደረጃጀት እንዲቀርቡ በማድረግ የስግብግብ ነጋዴውን ሴራ ማምከን ነው፡፡ ዘረፋውን መግታት መቻል ነው፡፡
ይህንን ሊቆጣጠር የሚገባው መንግስታዊ አካል ስራውን በተገቢው መንገድ በመስራት የተጣለበትን ኃላፊነት መወጣት አልቻለም፡፡ ገበያውን ማረጋጋት ሕብረተሰቡንም ከምዝበራ ሊታደገው አልቻለም፡፡ አለሁ ማለቱ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ኖሮም የፈየደው ነገር የለም፡፡ ተገቢ ቁጥጥር በሕገወጦች ላይ በማድረግ ሕጋዊ ቅጣት ማሳረፍ ቢችል ኖሮ እንዲህ አይን ያወጣ በደል በሕብረተሰቡ ላይ አይፈጸምም ነበር፡፡
የዚህ አካል ቸልተኝነት ምናልባትም በውስጡ ከነጋዴው ጋር የተመሳጠረ ኃይል መኖር ሕብረተሰቡን ለጉዳት አሳልፎ ሰጥቶታል፡፡ እንዲህ አይነት የሕዝብ ብሶትና ቅሬታ ሲጻፍ መልስ ለመስጠት ጊዜ አይፈጅባቸውም፡፡ ብዙ መስሪያ ቤቶች እንደዚሁ ናቸውና፡፡ ሕዝብንና መንግስትንም የቸገረው ነገር ይሄ ነው፡፡
ችግሩን ለመፍታት ጠንክሮ ከመስራት ይልቅ ማስተባበያ መስጠቱ የሕዝብን ችግር ብሶት ቅሬታ አይፈታውም፡፡ እንባውን አያብስለትም፡፡ በተግባር የሚታይ ለውጥ ለማምጣት ነው መስራት ያለባቸው፡፡ በተለያየ የገበያው ዘርፎች የሚታየው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪና ንረት ሆን ተብሎ የፖለቲካ ትኩሳቱን ለመጨመር ሲባል የሚደረግ የተቀነባበረ ሴራ ነው፡፡ ይሄ የትም ድረስ አያደርስም፡፡
በሕብተረተሰቡ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይፈጠር የሚሰራ የኢኮኖሚ አሻጥርና ደባ ሴራ ነው፡፡ ሕዝብን ከሕግ ውጭ በገበያ እያስመረረ እንዳሻኝ እከብራለሁ የሚል አስተሳሰብ በስፋት በነጋዴው ውስጥ ተንሰራፍቶአል፡፡ በየትኛውም አጋጣሚ ትንሽ ግርግር ሲፈጠር የሆነ ቦታ ረብሻ አለ ከተባለ የገበያውን ዋጋ በማሳደግ ሸቀጦችን ደብቆ ከገበያ በማጥፋት ጭንቅ ውስጥ የሚከተው ሕጻናት ለሚጠጡት ወተትና ሻይ ስኳርን በማጥፋት በዜጎች ላይ ቁማር የሚጫወተው ነጋዴው ነው፡፡ የእርሱ ልጆች ሻይ የሚጠጡበት ስኳር አላቸው፡፡ የሕዝቡ ልጆች ደግሞ እንዳያገኙ ይከለክላል፡፡ በሕጻናትና በአረጋውያን ሃዘን ይደሰታል፡፡ እንዲህ ባለ መልኩ የሚሰራው ስራ መጨረሻው አያምርም፡፡
ነጋዴው ሰርቶ አትርፎ መኖር የሚችለው ሰላምና ሕዝብ መኖር ሲችል ብቻ ነው፡፡ የሀገር ሰላም ነው ዋናው፡፡ ይሄንን በቅጡ የተረዳ ነጋዴ አይደለም ያለው፡፡ ሕዝብን በማስመረር መክበር መኖርም አይቻልም፡፡ የእህል ምርቶችን በተመለከተ ዘንድሮም እንደ አምናው ሁሉ ሀገሪቱ እጅግ ከፍተኛ ምርት ነው ያስመዘገበችው፡፡
በገበያው ላይ በርካሽ ዋጋ ለሕብረተሰቡ መሸጥ ሲገባቸው በየጊዜው ዋጋውን እየቆለሉ ሕዝቡን እያስለቀሱት በኑሮ ወድነት እያማረሩት ይገኛሉ፡፡ በጤፍ አምራች ሀገር በነጻ ገበያ ስም አንድ ደረቅ እንጀራ 5 ብር ሲገባ በእጅጉ አሳሳቢ አደገኛና አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ መሆናችንን ልብ ብለን ማስተዋል ይገባናል፡፡ ሽሮ በእንጀራ ባዶውን 18 ብር ሲሸጥ ይሄንን አድገት ነው ብሎ ለታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ብታስረዳ ሊገባው አይችልም፡፡ ስለሌሎች ነገሮች ብታስረዳውም አይቀበልም፡፡ መጀመሪያ በአነስተኛ ዋጋ የእለት ጉርሱን ማግኘት አለመቻሉ ነው እሱን የበለጠ የሚያማርረው፡፡ በእንዲህ አይነት ችግሮች መቀለድ አይቻልም፡፡ የመዝናናት ሳይሆን የመኖር ጥያቄ ነውና፡፡
የታችኛው የሕብረተሰብ ክፍል በጣም ዝቅተኛ በሆነ የእለት ስራ ገቢ እንዴት ነው ሊኖር የሚችለው ይህስ ሁኔታ ወደየት ይወስደናል ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ በየትኛውም ዓለም ላይ ርካሽ ሁኖ ገበያ ላይ በተለያየ ዋጋ ሕዝቡ እንደየአቅሙ በገበያ ላይ የሚያገኘው የምግብ እህልና የበሰለ ምግብን ነው፡፡
እኛ ጋ ደግሞ ምንም ሳይጠፋ በገበያ ላይ በሰው ሰራሽ ተንኮል የገበያ ውድነት በመፍጠር በየጊዜው ዋጋው እየጨመረ ሕዝብን እስከማስመረር የደረሰው የምግብ እህሎችና የበሰሉ ምግቦች ናቸው፡፡ ተቆጣጣሪና ሥርዓት የሚያሲዝ አካል ቢኖርም እንዳለ አይቆጠርም፡፡ መንግስት የሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ አልተወጣም፡፡
የኮንትሮባንድ ንግድ በከፍተኛ ደረጃ ተስፋፍቶአል፡፡ በስውር በሚሴረው ሴራ ጤፉም ስኳሩም ዘይቱም ሌላውም በስውር እየተጫነ ይወጣል፡፡ በተለያየ ጊዜ በፖሊስ የተያዙትን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ እዚህ ውስጥ የተለያዩ አካላት እጅ ከጀርባ እንደሚኖር ይታመናል፡፡ ሕግና ሥርዓት ማስያዝ የመንግስት ስራ ብቻ አይደለም፡፡ ተጠቂው ሰለባ የሚሆነው ሕዝቡ ስለሆነ መከላከል ያለበት ሕዝቡ ከመንግስት ጎን በመቆም ነው፡፡ መንግስት የኑሮ ውድነቱን ለመፍታት ዛሬም ጠንክሮ እየሰራ ይገኛል፡፡ የሕዝብን እገዛም በስፋት ይፈልጋል፡፡ ኮንትሮባንድ ነጋዴዎችን ከሕግ ውጭ እየሸጡ የሚያማርሩትን በማጋለጥ በመጠቆም ሕዝቡ ለራሱ ሲል ከመንግስት ጎን መቆም ይጠበቅበታል፡፡

 

መሐመድ አማን

Published in አጀንዳ

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በጥልቀት ለገመገመ ሁለት መንገዶች ከፊት ለፊት እንደሚጠብቋት በግልጽ መገንዘብ ይቻለዋል፡፡ በአንድ በኩል ለዘመናት ካንቀላፋችበት በመንቃት መሰናክል ቢገጥመው የሚያስቆጭ ለውጥ በማስመዝገብ ላይ የምትገኝበትን መንገድ መጓዝ ጀምራለች፤ በሌላ በኩል ደግሞ የመሳካት እድሉ እጅግ ዝቅተኛ ቢሆንም አፍራሽ የሆኑ አመለካከቶችና ድርጊቶች የሚፈታተናት በውስጥና በውጭ ባላንጣዎቿ ወደ ተበታተነች አገር የሚወስድ መንገድ የተደገሰላት አገር ትታያለች፡፡
አገር በእንዲህ አይነት መንታ መንገድ ላይ በቆመችበት ወቅት የመፍትሄው አካል በመሆን ረገድ የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሚና ወሳኝና አስፈላጊ ቢሆንም፤ የልሂቃን ተሳትፎ ግን የላቀ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ፊደል ከመቁጠር የተገኘው እውቀት፣ የሌሎችን አገራት ተሞክሮ ማብራራት የሚያስችል ምሁራዊ አስተያየት እንዲሁም አማራጭ የመፍትሄ መንገዶች ማመላከት የሚያስችል ልምዶች ስላላቸው ነው፡፡
ምሁራን በአገር ዴሞክራሲዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት እንዲሁም በሰላም እሴት ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ተወጥተዋል ብሎ ለጠየቀ በቂ አለመሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ለእዚህም በምሁራኑ ዘንድ ክፍተት ይታያል ከሚለው የመንግስት ወቀሳ እና መንግስት ምህዳሩን በበቂ ሁኔታ በማመቻቸት ረገድ የሚያሳየው ውስንነት ለችግሩ በር ከፍቷል በሚል የሚሰጠው የምሁራኑ ምላሾች እንደ ምክንያት ሊቀርብ ይችላል፡፡
በሁለቱም ወገን የሚንጸባረቀው መወቃቀስ መቋጫ አግኝቶ ልሂቃኑ በአገር ግንባታ የሚኖራቸው ሚና እንዲጎላ በቅንነት ክፍተቶችን ፈትሾ መፍትሄ ማስቀመጥ ተገቢ ነው፡፡ በእዚህ ረገድ መንግስት የሚያወጣቸው የልማት ፖሊሲዎች፣ የዲፕሎማሲ፣ የደህንነት አቅጣጫዎች እና ሌሎችም ትላልቅ አገራዊ አጀንዳዎች ላይ ውሳኔ ከማሳለፉ በፊት የእነርሱን ተሳትፎ ማሳደግ ይጠበቅበታል፡፡ ምሁራኑ ያለ ፖለቲካዊ ርዕዮተ አለም ልዩነት የሚሳተፉበት መድረኮች ተመቻችተው የሀሳብ ልዕልና የበላይነት የሚያገኝበት እና በግብዓትነት ተወስዶ ለአገር ግንባታ የሚውልበት እድል ሊሰፋ ይገባል፡፡
የተለየ ሃሳብ የሚያንጸባርቁ ምሁራንን እንደ ተቃዋሚ ወይም የእነርሱን አመለካከት እንደሚያንጸባርቁ ‹‹አክቲቪስት›› አድርጎ የመፈረጁ ዝንባሌም ካለ አሁኑኑ ሊገታ ግድ ይላል፡፡ ሃሳብን ማሸነፍ የሚቻለው በተሻለ ሃሳብ እንጂ በጭፍን ፈርጆ በማግለል ስላልሆነ ከማንም ይምጣ ከማንም በትክክለኛነቱ ብቻ መዝኖ መውሰድ ይገባል፡፡ ሃሳብን ለአገር ግንባታ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ከግምት በማስገባት ለችግሮች ከሚሰጠው መፍትሄ አንጻር እንጂ ከሚያቀርበው ወገን ማንነት ጋር ማያያዙ ጠቃሚም አስፈላጊም ባለመሆኑ መወገድ አለበት፡፡
በምሁራኑ ዘንድ የሚታየው ሽሽትም መፍትሄ የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይም ፍረጃን በመፍራት የልሂቃንነት ሚናቸውን ሳይወጡ ‹‹የጋን ውስጥ መብራት›› በመሆን የሚኖሩ አሉ፡፡ በአንድ ወገን መንግስት የሚከተለውን አቅጣጫ ደግፈው ቢናገሩና ቢጽፉ በመንግስት ደጋፊነት በሌላም በኩል በነቃፊነት ጎራ ቢሰለፉ በተቃዋሚ ጎራ እንፈረጃለን የሚለው ስጋት ተጫጭኗቸው በዝምታ የሚቆዝሙ ምሁራን መኖራቸው አይካድም፡፡ ለእዚህ አቢይ ማስረጃ የሚሆነው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ሲጠየቁ ፍረጃን ብቻ በመፍራት የሚያሳዩት ቁጥብነት ነው፡፡
ምሁራን እንደ ምሁር በአመክንዮ ትክክል የሚሉትን በድፍረት በማንጸባረቅ የሚመጣውንም ፈታኝ ነገር መቋቋም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለሚያምኑበት አላማና እውነት በግልጽ የሚታገሉና ስህተት እንዳይፈጠር አስቀድሞ የሚያሳውቁ፤ የተሳሳተውን የሚያስተካክሉ ያጠፋውን የሚያርቁ የተሻለ ሃሳብ የሚያፈልቁ ምሁራን ያስፈልጉናል፡፡
በርካታ ሊሂቃን የሚገኙባቸው ዩኒቨርሲቲዎቻችን ከተሰጣቸው ተልእኮዎች አንዱ ምርምር ማድረግ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሁራን የሚደረጉ ምርምሮች በአገሪቱ ነባራዊ ችግሮች መነሻነት አገራዊ መፍትሄ የሚጠቁሙ ሊሆኑ ይገባል፡፡ የሌሎች አገራት ተሞክሮዎችም በመፍትሄነት ሲጠቀሱ ከነባራዊ ሁኔታው ጋር ምን ያህል የተጣጣሙ ናቸው የሚለው መፈተሽ አለበት፡፡ ከምንም በላይ ግን የምሁራን የጥናት ስራዎች ከመደርደሪያ ማሞቂያነት አልፈው ችግሮች በሚታዩባቸው መስኮችና አካባቢዎች በመፍትሄነት ሲተገበሩ ማየት ወሳኝ ነው፡፡
አገር በመላው ዜጎች ተሳትፎ ትገነባለች፤ ሁሉም በተማረበት፣ የስራ ልምድ ባካበተበት እና በተሰማራበት መስክ በሚያደርገው አስተዋጽኦ በተባበረ ክንድ ወደ ብልጽግና ታመራለች፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ሰላም የሰፈነባት፣ ዴሞክራሲዊ ሥርዓት የበለጸገባትና በእድገቷ ሁሉንም ዜጎቿን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተጋች በምትገኝበት ነገር ግን በጊዜአዊ ችግሮች እየተፈተነች ባለችበት በአሁኑ ወቅት ብዙ የተደከመባቸው እና ብዙ የሚጠበቅባቸው ልሂቃን ተሳትፎ የላቀ መሆን እንዳለበት ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ለእዚህም የዜግነት እና የምሁርነት ድርብ ሃላፊነታቸውን ይወጡ፡፡

 

Published in ርዕሰ አንቀፅ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።