Items filtered by date: Saturday, 10 February 2018
Saturday, 10 February 2018 23:53

ጓደኝነት የት ድረስ?

ልጆች እንዴት ናችሁ? የሳምንቱ የትምህርት ጊዜ እንዴት አለፈ። አሁንማ ትምህርቱም ሞቅ ሞቅ ብሎ ተጀምሯል አይደል? የመጀመሪያውን መንፈቅ ዓመት ፈተና ተፈትናችሁ ጥሩ ውጤት እንዳመ ጣችሁ አልጠራጠርም። ዛሬ አንድ ታሪክ ልነግራችሁ ተዘጋጅቻለሁ። ምን መሰላችሁ የ7ተኛ ክፍል ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ያጋጠመኝ ነው። ታሪኩን ያጫወ ተችኝ ደግሞ እንደ ነፍሴ የምወዳት አያቴ ነች። የብዙዎቻችን መሰረቶች እኮ አያቶቻችን ናቸው አይደል?

ከዕለታት በአንደኛው ቀን ከትምህርት ቤት በጣም ደክሞኝ እና ተደብሬ ተመለስኩ። በቤታችን ግቢ ውስጥ በሚገኝ አንድ ዛፍ ስር አያቴ ከፀሐዩ ተከልላ ተቀምጣለች። ከቤተክርስቲያን መልስ እቤት ከመግባቷ አስቀድማ በዚህ ጥላ ስር አረፍ ማለት ትወዳለች። በዚህ ወቅት በሩን ከፍቼ ወደ ውስጥ ስዘልቅ ከአያቴ ጋር ፊት ለፊት ተገጣጠምን። ሁል ጊዜ በፊቴ ላይ በምታየው ነገር እንደተደሰትኩ፣ እንደተ ከፋሁ ወይም ጥሩ ስሜት እንዳል ተሰማኝ ታውቃለች። አብዛኛውን ጊዜ ከጓደኞቼ ጋር ስሆን ነው ይህን ዓይነት ስሜት የምታስተውልብኝ። እንደዚህ ዓይነት አጋጣሚ ላይ ደግሞ ቆንጆ ቆንጆ ታሪኮችን ታወጋኛለች። እስቲ ምን ዓይነት ታሪክ እንደነበር ለናንተም ላጫውታችሁ።
አያሌው እና ቤተሰቡ በአንድ መንደር ውስጥ ይኖራሉ። ቤተሰቦቹ ደስተኞች እና ቀለል ያለ ኑሮ የሚኖሩ ናቸው። ቤታቸውን ከረጀም ጊዜ በፊት ነበር የገዙት። ያን ጊዜ ቤቱ በጣም የሚያምር እና አዲስ ነበር። በዚህ ቤት ከ10 ዓመት በላይ ኖረውበታል። አሁን ግን ቀለሙ ደብዝዟል። ከእንጨት የተሠሩት ግድግ ዳዎቹ እና በሮቹ መፋፋቅ እና ጭረት ይታይባቸዋል። በዚህ የተነሳ አያሌው ቤቱን ከእንደገና ለማደስ እና ቀድሞ ወደነበረበት ውበት ለመመለስ ፈለገ። ለልጁ እና ለባለቤቱ ሃሳቡን ነግሯቸውና ይደግፉት እንደሆነ ጠየቃቸው። እነርሱም የሱን ሃሳብ አንደሚጋሩት ነግረውት በሁኔታው ተስማሙ። በዚያ ላይ ልጃቸው በማደጉ አዲስ መኝታ ቤት ለግሉ ያስፈል ገው ነበር። ሁኔታው ይህንን እንዲያ መቻቹም ዕድሉን ፈጥሮላቸው ነበር።
አያሌው የህግ ባለሙያ ቢሆንም የአናፂነት ችሎታ ነበረው። የራሱን ቤት ለማደስም ያን ያክል አልተቸገረም ነበር። ባለቤቱ እና ልጁም በእድሳቱ ላይ አያሌውን እያገዙት ነበር። ሁሉም እርስ በርስ በጣም ስለሚዋደዱ አንቺ ትብሽ አንተ ትብስ ተባብለው ነበር ሥራቸውን የሚያከ ናውኑት።
አያሌው እና ቤተሰቡ አብዛኛውን የቤቱን ክፍል በሚያምር ሁኔታ አደሱት። አዳዲስ ዲዛይን በመጠቀም ቆንጆ ቤት እንዲሆን አድርገውት ነበር። የሳሎኑ ቤት እንደቀራቸውም ቤተሰቡ በምን ዓይነት ሁኔታ መታደስ እንዳለበት ለመወያየት ወሰኑ። አያሌው ለልጁ እና ለሚስቱ እንዲህ ሲል ሃሳብ አቀረበላቸው «ሳሎኑ ቤት ለረጅም ሰዓት ጊዜያችንን እናሳል ፋለን። ስለዚህ ይህኛውን ክፍል ከሌሎቹ በተለየ ቆንጆ ማድረግ ይኖርብናል። በዚያ ላይ የሳሎኑ የእንጨት ግድግዳ ስላረጀ በሙሉ ማንሳት ይኖርብናል።» ባለቤቱ እና ልጁ አያሌው ባቀረበው ሃሳብ ሙሉ ለሙሉ ተስማሙ ሥራቸውንም በጋራ ማከናወን ጀመሩ።
የሳሎኑን ግድግዳ በሙሉ ማንሳት ጀመሩ። በመሀል ግን አንድ ያልጠበቁት ነገር ተከሰተ። አያሌው በግራ በኩል ያለውን ግድግዳ በማንሳት ላይ እያለ አንድ እንስሳ ተመለከተ። ይህ እንስሳ እንሽላሊት ነበር። የሚያስገርመው ደግሞ እንስሳው ከግድ ግዳው ጀርባ መቀመጡ ነበር። ምክንያቱም ምንም ዓይነት መንቀሳቀሻ ቦታ ለእንሽላሊቱ አልነበረም። በዚያ ላይ በሚስማር ከውጪ በኩል እግሩ እንዲጣበቅ ሆኖ ተመቷል። በዚህ የተነሳ ይህ እንሽላሊት ወዴትም መሄድ አይችልም ነበር። በሁኔታው የተገረመው አያሌው መቼ ሚስማሩ በእግሩ ላይ እንደተመታ እና ሊያጣብቀው እንደቻለ አሰበ። አያሌው ከወራት በፊት አንድ ፎቶ ለመስቀል ነበር ይህን ሚስማር የመታው። ሁኔታውን ሲያስታውስ ደግሞ ይበልጥ ተገረመ።
አያሌው የእንሽላሊቱን ሁኔታ ለልጁ እና ለሚስቱ ጠርቶ አሳያቸው። ሁሉም በሆነው ነገር ተገረሙ። በጣም ያስደነ ቃቸው ነገር ደግሞ እንዴት ይህ እንሽላሊት ምንም ምግብ ሳያገኝ በዚህ ሁኔታ መቆየት እንደቻለ ነበር። ሁሉም እርስ በርስ ተያይተው እንሽላሊቱ ባጋጠ መው ነገር እጅግ አዘኑ። ትንሽ ጠብቀ ውትም የሚሆነውን ነገር ለመከታተል ወሰኑ። ምንም ምግብ ሳያገኝ እንሽላሊት ይህን ያክል ጊዜ መቆየቱ አስገራሚ ነበር።
ግድግዳውን ማስተካከል ትተው በሌላ ሥራ ተጠመዱ። በድንገት የአያሌው ልጅ አንድ ነገር ተመለከተ። ሌላ ሁለተኛ እንሽላሊት ነበር በግድግዳው ላይ ያየው። «አባዬ እማዬ አያችሁት ሌላኛውን እንሽላሊት» ሲል ጮኸ። ሁሉም ዓይና ቸውን የሳሎኑ ግድግዳ ላይ እንደተከሉ አዲስ የመጣውን እንሽላሊት መመልከት ቻሉ። ይህ እንሽላሊት በአፉ ምግብ ይዞ ነበር። ሁኔታው በጣም የሚያስገርም ነበር። የያዘውንም ምግብ ለተጣበቀው እንሽላሊት ሲመግበው ተመለከቱ። ሁኔታው ከማስገ ረመም ባለፈ በጣም የሚያሳዝን ነበር። ምክንያቱም ለወራት በግርግዳው ላይ የተጣበቀውን ጓደኛውን ምንም ሳይሰለች ምግበ ይመግበው ነበር። ጓደኛው አንድ ቀን ከገባበት ችግር ውስጥ እንደሚወ ጣ በማሰበ አንድ ዕድል እስኪመጣ ድረስ ተስፋ ሳይቆርጥ እገዛውን ያደረግለት ነበር። ይህ ተስፋ ሲያደርጉበት የነበረው ቀን ደርሷል። አያሌው እንሽላ ሊቱን ከገባበት ችግር አላቆለት ሁለቱም እንሽላሊቶች ተከታትለው ወደ መኖሪያ ቸው ሄዱ።
እነ አያሌው ሳሎኑን ከሌሎቹ ክፍሎች በተለየ መልኩ ቆንጆ አድርገው አደሱት። ዕቃዎቻቸውንም በሙሉ አስተካክለው እንደ ጨረሱ ሶፋው ላይ ቁጭ አሉ። ቤታቸውንም አሳምረው በማደሳቸው ሁሉም ደስተኞች ሆነዋል። ከምንም ነገር በላይ ደግሞ በሳሎኑ ውስጥ የተመለከቱት የእንሽላሊቶቹ ትእይንት በጣም ነበር ያስገረማቸው። ከዚያም አልፎ ትልቅ ትምህርት ሰጥቷቸው አልፏል። አያሌው ያጋጠማቸውን ነገር አስታውሶ ለባለቤቱ እና ለልጁ እንዲህ አላቸው «የእንሽላሊቶቹ ታሪክ ለኛ ትልቅ ትምህርት ነው። እያንዳንዳችን በሚያጋጥመን ችግር ላይ መደጋገፍ ይኖርብናል። ሁሉንም እን ደቤተሰብ በጋራ መወጣት አለብን። ምንም ያህል ጊዜ አንዳችን ችግር ውስጥ ብንገባ በጎ ቀን እስኪመጣ እንደ እንሽላ ሊቶቹ ህብረት መፍጠር ይኖርብናል» አላቸው። ሁሉም በአንድነት ለራሳቸው በእያንዳንዱ ችግር ውስጥ አንድ ላይ ለመሆን ቃል ገቡ።
ልጆች እናንተስ ለጓደኞቻችሁ ያላችሁ ግምት ምን ዓይነት ነው? ዝም ብሎ ለጨወታ ጊዜ ብቻ? ተገናኝቶ መለያየት? ወይስ ችግር በሚያጋጥማቸው ጊዜ መረ ዳዳት እንዳለባችሁ ታምናላችሁ? «በደስ ታም ሆነ በችግር ጊዜ አብሮ መሆን የመል ካም ጓደኛ መገለጫ ነው» ብላችሁ የምታ ስቡ ከሆነ በጣም ትክክል ናችሁ። ወደፊትም ለጓደኞቻችሁ ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቦቻ ችሁም ጭምር መልካምና አሳቢ ልትሆኑ ይገባል እሺ። እኔ ለዛሬ የነገርኳ ችሁን ታሪክ ጨርሻለሁ በሚቀ ጥለው ጊዜም ከሌላ ታሪክ ጋር እንገና ኛለን። መልካም የዕረፍት ቀን እና የትምህርት ዘመን ይሁንላችሁ። ሰላም!

Published in ማህበራዊ

በአፍሪካ እግር ኳስ ታሪክ ከታዩ ድንቅ ባለ ተሰጥኦ የአጥቂ መስመር ተጫዋቾች መካከል ራሺድ ያኪኒ አንዱ ስለመሆኑ በርካቶች ይስማማሉ፡፡ የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን የምን ጊዜም ኮኮብ ግብ አስቆጣሪው አረንጓዴ ንስር በአሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ የህልፈተ ህይወቱ ዜና ከተሰማ አንድ ሳምንት ተቆጥሯል፡፡ ከኳስ ውጪ ሌላ ህይወት እንዳልነበረው የሚነገርለት ጭምቱ ኮከብ ጫማውን ከሰቀለ በኋላ የነበረው ህይወትና የሞተበት መንገድ ያለፈው ሳምንት የስፖርት ቤተሰቡ መነጋገሪያ ሆኗል። 

የያኪኒን ጉዳይ በተመለከተ የተለያየ ምርመራና ክትትል ሲያደርጉ የቆዩ የአሩ ናይጄሪያና ሌሎች ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በርካታ መረጃዎችን በህይወቱ ዙሪያ እያወጡ ይገኛሉ፡፡ ያኪኒ ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል የኖረበትን የእግር ኳስ ህይወት በአገሩ ሊግ የጀመረ ቢሆንም በቀጣይ ያመራው ወደ ኮትዲቯሩ ክለብ አፍሪካ ስፖርት ናሽናል ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ለህይወቱ ማለፍ ምክንያት ተደርጐ የሚጠቀሰው ጉዳይም ከዚህ ይጀምራል፡፡
ያኪኒ በኮትዲቯሩ ክለብ በነበረው ቆይታ የሚያገኘውን ገንዘብ በራሱ ስም በባንክ የሚያስቀምጥ ሰው አልነበረም፡፡ ይልቁንም በትውልድ አገሩ በናይጄሪያ ቤቱን ለሚጠብቅለት የቅርብ ጓደኛው በመላክ እንዲያስቀምጥለት ያደርግ ነበር፡፡ ይህ ጓደኛውም የሚልክለትን ገንዘብ ተቀብሎ እቤቱ ውስጥ ሲያጠራቅምለት ይቆያል፡፡ ከእለታት አንድ ቀን ግን ይህ ጓደኛው የተጠራቀመው ገንዘብ ልቡን አሸፍቶት ከኮከቡ ጓደኛው ይልቅ ንዋይን መረጠ። ያኪኒ የኮትዲቯር ቆይታውን ደምድሞ ወደ አገሩ ሲመለስም ጓደኛው ከድቶት ቅንጡ መኪናና ቤት ገዝቶ የተንደላቀቀ ህይወት ሲመራ ተመለከተው። ከዚህ ጊዜ አንስቶም ያኪኒ ሰውን መራቅና ብቸኝነትን ከመምረጥ ባለፈ ማንንም ማመን አቆመ፡፡ የያኪኒ ህይወት ግን በዚሁ አላበቃም። ሌላ ተስፋና ሌላ ህይወት የጀመረበትን አጋጣሚ ከወደ አውሮፓ አገኘ፡፡ ፖርቹጋል፤ ግሪክና ሌሎች በርካታ አገራት ተዘዋውሮ በመጫወትን በራሱ ላብ በክህደት ያጣውን ገንዘብ መልሶ አገኘው፡፡ ገንዘቡን ብቻም ሳይሆን ጫማውን ሰቅሎ ወደ አገሩ ሲመለስ አንድ የሚቀርበውና የሚያምናው፤ ቀድሞ በጓደኝነት የተሰበረ ልቡን የሚጠግንለት አዲስ ጓደኛ አገኘ፡፡ እንደ ማንኛውም ስፖርተኛ ያኪኒ ከስፖርት ሲገለል ወደ ቢዝነሱ ዓለም ገብቶ ቀሪ ህይወቱን ለማሳለፍ ከአዲሱ ታማኝ ጓደኛው ጋር አንድ መላ ዘየዱ። ጓደኛው እውቀቱን ያኪኒም ሙሉ ጥሪቱን አሟጦ የጌጣጌጥ ንግድ ለመጀመር ዝግጅታቸውን ጨረሱ። ያኪኒ ውድ የሆኑ ሃብቶቹን በመሸጥ ጭምር ቢዝነሱን ለመጀመር ለጓደኛው ገንዘቡን ባስረከበበት ወቅት ግን አንድ አስደንጋጭ ክስተት ተፈጠረ። በቅርብ ሲከታተሏቸው የነበሩ ዘራፊዎች ጓደኛውን እቤት ውስጥ ገድለው ጠቅላላ ገንዘቡን ይዘው ተሰወሩ። አሁን ያኪኒ ልቡ ክፉኛ ተሰበረ፤ ያመነው ጓደኛው ከዳው፤ የታመነለት ደግሞ በዘራፊዎች ተገደለ፤ ይህም ቅስሙን ሰበረው። ብቸኝነቱን መርጦም ልጆቹን ጨምሮ ዘመድ አዝማዱን ርቆ አሁን ህይወቱ በአርባ ስምንት ዓመቱ ባለፈበት ትንሽ ከተማ ኢባዳን መኖርን መረጠ።
ያኪኒ በዚህች ከተማ ህይወቱን መምራት በጀመረበት ወቅት ይታይበት የነበረው ያልተለመደ ባህሪን ተከትሎም ነበር የመገናኛ ብዙሃን እይታ ውስጥ የገባው። ያኪኒ በዚህ ወቅት እጅግ ብቸኛ ከመሆኑ ባሻገር የአዕምሮ እክል ገጥሞት እንደነበር መረጃዎች ወጥተዋል። ሲከታተሉት የነበሩ የናይጄሪያ መገናኛ ብዙሃን ያኪኒ የቅርብ ቤተሰቦቹን ጭምር እቤቱ ሲመጡ ያባርራቸው እንደነበር ዘግበዋል። ከዚህ በባሰም መንገድ ላይ ጭምር ሲፀዳዳና የቤቱን ቁሶች ግቢው ውስጥ ሲያቃጥል እንደታየም ተነግሯል።
ያኪኒ ከዚህ ካልተለመደ ባህሪው ባሻገር በአካባቢው ያሉ ሰዎችና ጎረቤቶቹ የአዕምሮ ችግር እንዳልነበረበት አስተያየት ሲሰጡ ተደምጠዋል። እንዲያውም ያኪኒ በአካባቢው ካሉ ድሃ ማህበረሰቦች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንደነበረውና ከገንዘብ አንስቶ እስከ ሚመገቡት ሩዝ ሲያከፋፍል እንደኖረ ይናገራሉ። ይህም የእውነት ያኪኒ የአዕምሮ ችግር ነበረበት ወይስ የደረሰበት ስነ ልቦናዊ ጉዳት ራሱን ከቅርቦቹ ሰዎች እንዲያገል አደረገው የሚል ውዝግብ እንዲነሳ አድርጓል።
ይህ በአንድ ወቅት በዓለማችን እግር ኳስ ታላቅ የነበረ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች አሁን የህይወቱ ፍፃሜ በአሳዛኝ መልኩ ተቋጭቷል። የአረንጓዴ ንስሮቹ ታሪካዊ አጥቂ መጨረሻው ባያምርም በእግር ኳሱ የሰራቸው ታሪኮች ዘመን ተሻጋሪ ሆነው ይታወሳሉ። እኤአ 1963 ናይጄሪያ ካዱና ውስጥ የተወለደው ያኪኒ በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች በመጫወት ያን ያህል የጎላ ስም ባይኖረውም በናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ያኖረው ታሪክ ግን አረንጓዴ ንስሮቹ እስካሁን ካፈሯቸው ታላላቅ ተጫዋቾችም የጎላ ነው።
ያኪኒ ለናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ በተጫወተባቸው ሃምሳ ስምንት ጨዋታዎች ሰላሳ ሰባት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ባለ ክብረወሰን ነው። ያኪኒ በዓለም እግር ኳስ አፍካሪዎች ዘንድም የሚታወስባቸው በርካታ ታሪኮች ያሉት ኮከብ ሆኖ ይታወሳል። በተለይም አገሩ ናይጄሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ መድረክ ተሳትፋ ቡልጋሪያን ሦስት ለዜሮ በረታችበት የመጀመሪያ ጨዋታ ያኪኒ ለናይጄሪያ በታሪክ የመጀመሪያዋን የዓለም ዋንጫ ግብ ማሳረፉ ይታወሳል። ይህችን ግብ ካስቆጠረ በኋላም የግቡን መረብ ይዞ እያለቀሰ ደስታውን የገለፀበት መንገድ እስካሁንም በታሪክ የ1994 ዓለም ዋንጫን እንዲታወስ ያደርጋል። እኤአ 1993 ላይ የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ የተሰየመው ያኪኒ ለናይጄሪያ ብሄራዊ ቡድን በሁለት የዓለም ዋንጫና በሦስት የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች ተሰልፎ መጫወት ችሏል። አረንጓዴ ንስሮቹ የ1994 አፍሪካ ዋንጫን ሲያነሱም ያኪኒ የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ በመሆን ቁልፍ ሚና ነበረው። እኤአ በ1988 የሲዎል ኦሊምፒክም በናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ መካተቱ ይታወሳል።

ቦጋለ አበበ

Published in ስፖርት

መዳረሻውን በስድስት ከተሞች ያደረገው የዘንድሮ ዓመት የዙር የቤት ውስጥ ውድድር ከሳምንት በፊት ተጀምሯል። የውድድሩ ድምቀት የሆነችው ኢትዮጵያዊት አትሌት ገንዘቤ ዲባባም በድል ተንበሽብሻ ቀጥላለች። ውድድሩ ከሳምንት በፊት በጀርመኗ ከተማ ካርሹር ሲጀመር በገነነችበት በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ጣፋጭ ድል ያጣጣመችው ገንዘቤ የውድድሩ ሦስተኛ መዳረሻ ከተማ በሆነችው የስፔኗ ማድሪድ በአምስት ቀናት ልዩነት ሌላ ድል አስመዝግባለች። 

ውድድሩ ከትናንት በስቲያ ሲካሄድ ሃያ ሰባተኛ ዓመቷን በድል ያከበረችው ገንዘቤ የተጠበቀውን ያህል ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ ባትችልም በውድድር ዓመቱ ምርጥ አቋም ይዛ እንደተመለሰች አስመስክራለች። በኮሎምቢያዊቷ አሯሯጭ ሙሬል ኮኖዮ የተጀመረው የአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ውድድር የመጀመሪያው አራት መቶ ሜትር የተገባደደው 1፡03፡21 በሆነ ሰዓት ሲሆን ስምንት መቶ ሜትሩም የተገባደደው ፈጣን በሆነ 2፡07፡50 ነበር። ውድድሩ በዚህ ርቀት ላይ እያለ የራሷን ምርጥ ሰዓት የሆነውን 4፡04፡00 ለማሻሻል ከፍተኛ ፉክክር ስታደርግ የነበረችው ጀርመናዊቷ ኮንስታንዝ ክሎስተርሃፈን ከገንዘቤ ዲባባ በአስር ሜትር ርቀት ላይ ስትከተል ነበር። ይህም የውድድሩ መጨረሻ በሁለቱ አትሌቶች ፉክክር ይደምቃል ተብሎ እንዲታሰብ አድርጎ ነበር። ይሁን እንጂ ከዚህ ርቀት በኋላ አሯሯጯ አትሌት መውጣቷን ተከትሎ ገንዘቤ ከአምስት ቀናት በፊት እንደነበራት ውድድር ፍጥነቷን ጠብቃ ወይንም ጨምራ መጓዝ አልቻለችም። ገንዘቤ የመጨረሻ ዙሯን ስትሮጥ ሰዓቱ 3፡29 ያመለክት ነበር። ይህም ከ4፡00 በታች የምትሮጥበት ሌላ አጋጣሚ ከእጇ እንደወጣ የሚያመላክት ስለነበር የመጨረሻ ዙሯን በተሻለ ፍጥነት ለማገባደድ ተስፋ እንዳይኖራት አድርጓል። ያም ሆኖ ግን የሦስት ጊዜ የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና አሸናፊዋ ገንዘቤ ዲባባ የቦታውን ክብረወሰን በሰበረ 4፡02፡43 ሰዓት አንደኛ ሆና ማጠናቀቅ ችላለች። ሰዓቷን ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት ያደረገችው ክሎስተርሃልፈን 4፡04፡72 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆና ውድድሩን ፈፅማለች። ይህም ያሰበችውን የራሷም ምርጥ ሰዓት በሰባት ሰከንድ ዘግይታ ሳታሻሽል እንድትቀር አድርጓታል። በአንፃሩ እንግሊዛዊቷ ኤሊሽ ማክኮልጋን ሦስተኛ ሆና ብታጠናቅቅም ያስመዘገበችው 4፡08፡07 ሰዓት የቤት ውስጥ ውድድር ምርጥ ሰዓቷ ሆኖ ሊመዘገብላት ችሏል።
ገንዘቤ ባለፈው እሁድ ካርሹር ላይ በነበራት የመጀመሪያ ውድድር 3:57.45 ሰዓት በማስመዝገብ የዓመቱን ፈጣን ሰዓት የግሏ ከማድረጓ ባሻገር ያስመዘገበችው ሰዓት በቤት ውስጥ ውድድር ሁለተኛው የዓለማችን የአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ፈጣን ሰዓት ሆኗል። ገንዘቤ በዚህ ውድድርና ርቀት የመጀመሪያው ፈጣን ሰዓትም የራሷ ሲሆን ከአራት ዓመት በፊት እዚሁ ከተማ ላይ 3:55.17 የሆነውን ክብረወሰን ማስመዝገቧ ይታወሳል። ይህንንም ሰዓት ከገንዘቤ ውጪ ዳግመኛ በሁለት ሰከንድ እንኳን የተጠጋ ሌላ አትሌት የለም። ከሁለት ዓመት በፊትም እዚሁ ውድድር ላይ 4:00.13 ሰዓት ማስመዝገብ ችላለች። ይህም ሰዓት አሁን ላይ የዓለማችን አስረኛው ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት በቤት ውስጥም ከቤት ውጪም ባሉ መካከለኛና ረጅም ርቀቶች በርካታ የዓለም ክብረወሰኖችን በቀናት ልዩነት ሳይቀር የግሏ ማድረግ የቻለችው ገንዘቤ በ2017 የውድድር ዓመት መጀመሪያ የሁለት ሺ ሜትር የቤት ውስጥ የዓለም ክብረወሰንን ሳባዴል ላይ 5፡23፡75 በማስመዝገብ መስበሯ አይዘነጋም።
በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር የቤት ውስጥ ውድድርም የዓመቱን መሪ ሰዓት መያዝ ችላ ነበር። ይህም በአስራ ስድስተኛው የለንደኑ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በርካታ ኢትዮጵያውያን ውጤት እንዲጠብቁባት አድርጓል። ይሁን እንጂ ገንዘቤ በቻምፒዮናው ላይ የተጠበቀባትን ብቃት ማሳየት ተስኗት በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ከግማሽ ፍፃሜ የማጣሪያ ውድድር በላይ መጓዝ እንዳልቻለች ይታወሳል።
ከለንደኑ የዓለም ቻምፒዮና በኋላ ከውድድር ርቃ የቆየችው ገንዘቤ አሁን አድናቂዎቿንና የአትሌቲክሱን ቤተሰብ ለመካስ ለእሷ ምቹ ወደ ሆነውና ደጋግማ ወደምታሸንፍበት የቤት ውስጥ ውድድር ተመልሳለች። ይህም በመጪው የካቲት በበርሚንግሃም ሲቲ በሚካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ላይ ለመሳተፍ እንደ ዝግጅት ይጠቅማታል ተብሎ ይጠበቃል።
የ2015 የዓመቱ ኮከብ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተለያዩ የዓለም ክብረወሰኖችን የግሏ በማድረግ ያሳየችውን ድንቅ ብቃት ዘንድሮም በጥሩ ጤንነት ላይ ከተገኘች ልትደግመው እንደምትችል በርካቶች ያምናሉ። ባለፉት ሁለት ዓመታት በአማካኝ በአንድ ዓመት ሦስት የዓለም ክብረወሰኖችን በማሻሻል አድናቆት አትርፋለች። ባለፉት ሁለት ዓመታት የቤት ውስጥ የዓለም ቻምፒዮናን የወርቅ ሜዳሊያ ከማሸነፍ በተጨማሪ በተለያዩ ርቀቶች በርካታ የቤት ውስጥ የዓለም ክብረወሰኖችን በእጇ ያስገባችው ገንዘቤ ፊቷን ከቤት ውጪ ወዳሉ ውድድሮች መልሳ የዓለም ቻምፒዮናን ክብርና የዓለም ክብረወሰንን ማሳካት ችላለች። ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል ተይዞ የቆየውን የአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ክብረወሰን አስደናቂ በሆነ 3፡50.07 ሰዓት መስበር የቻለችው ገንዘቤ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በቤጂንግ የዓለም ቻምፒዮና በርቀቱ በአትሌቲክስ ህይወቷ የመጀመሪያና ልዩ የሆነውን የዓለም ቻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቋ ይታወሳል። ይህ ተደጋጋሚ ስኬትም የዓመቱ ምርጥ ሴት አትሌት ሽልማት እንድትጎናፀፍ አስችሏታል።
ገንዘቤ ስቶክሆልም ላይ ሁለት የዓለም ክብረወሰኖችን ባለፉት ሁለት ዓመታት አስመዝግባለች። የአንድ ማይል ክብረወሰንም በገንዘቤ የመሰበር እድል እንዳለው ከወዲሁ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ገንዘቤ ይህን ክብረወሰን ካሳካች ስቶክሆልም ላይ ሦስት የቤት ውስጥ ክብረወሰኖችን በማሻሻል ከየትኛውም አትሌት የበለጠ ባለታሪክ ትሆናለች።
ካልሹር ተጀምሮ ከሦስት ቀናት በኋላ እዚያው ጀርመን ዱሴልዶርፍ ሁለተኛ መዳረሻውን ያደረገው የዘንድሮው ዓመት የዓለም የቤት ውስጥ የዙር ውድድር በሁለት ቀናት ልዩነት ከትናንት በስቲያ በስፔን ማድሪድ መዳረሻውን አድርጓል። በቀጣይም በአሜሪካ ቦስተንና በፖላንድ ቶረን ሲካሄድ የመጨረሻው ውድድር በፈረንጆቹ ሃያ አምስት ግላስጎ ላይ የሚደመደም ይሆናል።
በአንድ ወር ውስጥ በስድስት የተለያዩ ከተሞች በሚካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ የዙር ውድድር በሴቶች መካከል የሚደረገው ፉክክር እያንዳንዱ አትሌት በየውድድሩ የሚያስመዘግበው ነጥብ ተደምሮ አጠቃላይ አሸናፊው የሃያ ሺ ዶላር ተሸላሚ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪም አጠቃላይ አሸናፊ የምትሆነው አትሌት በበርሚንግሃም ሲቲው የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና በቀጥታ ተሳታፊ ትሆናለች።

 ቦጋለ አበበ

 

Published in ስፖርት
Saturday, 10 February 2018 19:43

አዞን - የቤተሰብ አባል

ከተለመዱት የቤት እንስሳት ውጪ አላምዶ በቤት አልያም በግቢ ማኖር የተዘወተረ ቢሆንም ምናልባትም ከፍተኛ አደጋ ሊያደርሱ ከሚችሉ አስፈሪ እንስሳት ጋር መኖር ግን ለአደጋ የሚያጋልጥና አስደንጋጭም ነው። የኢንዶኔዥያ ተወላጅ የሆነው ሙሀመድ ኢዋን ግን ለአንዳንዶቻችን እንኳን በአካል በፊልምም ለማየት የምንፈራውን አዞ የቤተሰቡ አባል አድርጎ 20 ዓመታትን ማሳለፉን ኦዲቲ ሴንትራል በዘገባው አስነብቦናል።
ሙሀመድ ኢዋን እ.ኤ.አ በ1997 ነበር በአንድ የባህር ዳርቻ ህጻናት ሲጫወቱበት ያየውን 25 ሴንቲ ሜትር ርዝማኔ ያለው የአዞ ግልገል ለያዙት ዓሣ አጥማጆች 25 ሺ የኢንዶኔዥያ ብር (ሩፒ) ከፍሎ ወደ ቤቱ ያመጣው። ዛሬ 20 ዓመት የሞላውና መሀመድ ኮጄክ እያለ የሚጠራው አዞ200 ኪሎ ግራም የሚመዝን ሲሆን 2ነጥብ 7 ሜትር ርዝማኔም አለው።
አዞ እወዳለሁ ኮጄክንም በጣም እንከባከበዋለሁ የሚለው መሀመድ የኮጄክ መኖሪያ የሆነውን ገንዳ በሳምንት አንዴ እንደሚያጸዳለትና ገላውንና ጥርሶቹንም እንደሚያጥበው ይናገራል። ኮጄክ ጥሩ የቤት እንስሳ እንደሆነ የሚናገረው መሀመድ ለምግቡም በሳምንት 50 ሺ ሩፒ የሚመደብለት ሲሆን፤ ከ1 ነጥብ 5 እስከ 5 ኪሎ የሚመዝኑ ዓሣዎችን እንደሚመግበው በመግለጽ «እኔን የሚያየኝ እንደአባቱ ነው» ይላል።
በአሁኑ ወቅት ኮጄክ ከአሜሪካ አውሮፓና አውስትራሊያ በሚመጡ እንግዶች የሚጎበኝ ሲሆን፤ በግቢው ውስጥ የ2 እና የ10 ዓመት እድሜ ካላቸው የመሀመድ ልጆች ጋር ሲንቀሳቀስ ማየት ጎብኚዎችን እያስደመመና እያዝናና ይገኛል። መሀመድ አንዳንድ ቱሪስቶች ኮጄክን እስከ 1 ሚሊዮን ሩፒ የኢንዶኔዥያ ብር የሚደርስ ገንዘብ አውጥተው ለመግዛት ቢጠይቁትም እሱ ግን እንደ አንድ የቤተሰቡ አካል ስለሚያየው ለመሸጥ ፈቃደኛ አለመሆኑንም ተናግሯል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

Published in መዝናኛ
Saturday, 10 February 2018 19:40

«ባምር ጠላሁ?»

«ከእናንተ የሚያስፈልገው መደራጀትና በመካከል ችግር ሊፈጥር የሚያሰኘውን /ያቆበቆበውንና የጠረጠራችሁትን መጠቆም ነው። በዚህ አሠራር እርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ ችግራችሁ ይቀረፋል...ቤት የሌለው ቤት ይገዛል፤ የጋራ መኖሪያ ቤት ዕዳ ያለበት ይከፍላል፤ ስኳርና ዘይት እንደልብ ታገኛላችሁ፤ መብራት ቢጠፋ እንኳ ጀነሬተር ቅርባችሁ ታደርጋላችሁ፣ ቡና ቁርስና ፀበል ጻድቅን ጨምሮ በቀን አራቴ ትበላላችሁ» ...እልልልልል...... ቸብቸብቸብቸብቸብ
...ሊቀመንበሩ ተናግሮ ይጨርስ አይጨርስ ሳይታወቅ አካባቢው በእልልታና ጭብጨባ ደመቀ። ሰዉ ይህን ያህል ቸግሮታል እንዴ? ጥቂቶች ብቻ ግን ሲያጉረመርሙ ነበር፤ እልል ባዮቹና አጨብጫቢዎቹ እነዚህ አጉረምራሚዎች ችግር የሚፈጥሩ ከተባሉት ውስጥ እንደሚሆኑ በደስታ ስሜት ውስጥ ሆነውም ጠርጥረዋል...።
ከአጉረምራሚዎቹ መካከል አንድ ጎልማሳ እጃቸውን አወጡ፥ «እድሉ ስላልተነፈገኝ አመሰግናለሁ...» ብለው ዙሪያቸውን ቃኘት አደረጉ፥ «እንግዲህ እኛም ቢሆን ማደጉን፣ መሻሻሉን፣ መለወጡን አልጠላን። እውነት ሊቀመንበር...ከልብዎ ከሆነ ተደራጁና ያ ሁሉ ነገር ይሟላላችኋል ያሉን መደራጀት አይደለም ድርጅት ሁሉ እናቋቁማለን» አሉ።
እንዲህ ያለ ጥያቄ ይሁን አስተያየት ግልጽ ያልሆነ ነገር በወረዳው ታሪክ ተጠይቆም ተሰጥቶም አያውቅም። ሰዉ ግራ ገባው ግን ደስታውና ከአሁኑ የሸመታ ሰልፉ ቀንሶ ፀሐይ ላይ መንቃቃቱ ሲቀነስለት ታይቶት፤ በተለይ እናቶችና ወጣት ሴቶች ማልደው ከቤት ወጥተው ሰልፉ ሳይደርሳቸው ምሳ ሰዓት ደርሶ ሲሯሯጡ፤ ሰልፉ ፊት ሲቃረቡና የልጅ ከትምህርት ቤት መውጫ ደወል ተደውሎ ሲሳቀቁ...ያ ሁሉ እልም ሲል ሲታያቸው ስለነበር መገረማቸው አልበለጠም።
«አዎን...ወንድማችን እንደተናገሩት...» ብለው ሊቀመንበሩ አስተያየታቸውን ሊሰጡ ሲሉ...
«አልጨረስኩም ሊቀመንበር...ባምር ጠላሁ? አለች ዝንጀሮ አሉ አያቴ፤ እንዲህ በምቾት ህልም የሚያንሳፍፉን በቅድሚያ ገንዘቡ የት አለ? እንደው እድገታችን ከሆድ ያላለፈ ይመስል ከአሁን አሁን አደግን ስኳርና ዘይት እንደልብ አገኘን እያልን ወር ከወር ስናሳድድ ይኸው የአየር ጸባይ እንኳ ተለዋወጠ...አስረጁንኮ ሊቀመንበር» አሉ፤ በዚህ ንግግር ለስብሰባው ቤተሰቡን ተክቶ የሄደ ወጣት ሲስቅ በእድሜ ከፍ ያሉ እናቶችና አባቶች ከንፈራቸውን መጠጡ።
ከዛ በኋላ የስብሰባው መንፈስ እንደነበር አልቀጠለም። ግራ በመጋባትና ሊቀመንበሩን ለማመን በመፈለግ የጎልማሳውን ሰው ንግግር እውነተኛነትም በማመን መካከል ሆነው ሁሉም ወደቤታቸው አቀኑ።
ከዛ የወረዳ ስብሰባ ወጣ ብለን ወዲህ እንምጣ፥ እኔ የምለው በእቅድና በተስፋ መካከል ልዩነት አለ ወይስ የለም? በእርግጥ አንድ ሰው ሲያቅድ፤ ባቀደው መልኩ ሃሳቡን እንደሚያሳካ ተስፋ በማድረግ ነው። ተስፋ የሌለው ሰው ምንም እንደሌለው ሊቆጠር ስለሚችል። ቢሆንም ሲያቅዱ በአንዳች ነገር ላይ ተመርኩዘው እንጂ በአየር ላይ ነው እንዴ?
አንድ የልጆች ተረት አውቃለሁ፥ በዶሮ እርባታ አንቱ የተባሉ ሰው ነበሩ። አንድ ቀን እጃቸው ለለጋስነት ተፈትቶ አንዲት እንቁላል ለልጅ ልጃቸው ሰጡት፤ ከዛ ቀደም ያልሆነና ከዛም በኋላ ያልተደገመ ልግስና። ልጁም እንቁላሏን ይዞ ከአያቱ ቤት እንደወጣ በእንቁላሉ ሊያደርገው የሚችለው ነገር ታየው።
ቤት ገብቶ እንቁላሏን ሙቀት ውስጥ ያስቀምጣታል፣ ቀስ ብላ ትፈለፈልና ጫጩት ያገኛል፣ ጫጩቷ ታድጋለች፣ ዶሮ ስትሆንለት ይሸጣትና ሌላ ብዙ እንቁላል ይገዛል፤ ብዙ ጫጩትም ያገኛል፣ ሁሉም ሲያድጉለት መልሶ የተወሰነውን ይሸጥና ኳስ ይገዛል፣ ኳስ ገዝቶ ጢባ ጢቤ ሲጫወት...ከሃሳቡ ብንን ይላል። ይህን ሁሉ ያለመባትን እንቁላል እግሩ ላይ ፍርጥ አድርጓታል...ከህልሙ ኳስ ጋር ተመሳስላበት።
አንዳንዴ ልክ እንዲህ ይሆናል፥ ተስፋ የሚያሳይ ሊቀመንበር ይኖራል...ሰላም ይመጣል፣ ስኳርም ይመጣል...መብራት ይመጣል የሚል። ልክ በዛ ህልም ወስዶን...ሰላም አለን ብለን ስንዝናና፣ ስኳር አለን ብለን ሻይ ቡና ስናበዛ፣ መብራት ይመጣል ብለን አብሲት ስንጥል...ብንን፤ ሌላ የተስፋ ጭላንጭል ለማሳየት ይሁን ባይታወቅም ሌላ ስብሰባ ይጠራል።
መቼ እለት ነው ይኸው ስኳር መሸመት የፈለገ እማወራና አባወራ ቀጥታ ከሱቆች እንዲገናኝ፤ ሸመታውም እንዲጧጧፍና ማንም እንዳይቸገር የሚል ሃሳብ በሚመለከተው አካል ቀረበ አሉ። ግን የከፋው ሃሳቡ ሳይሆን እቅድና ተስፋው በሌለ ስኳር ላይ መሆኑ ነው። መቼም የትኛውም አመራር መንፈሳዊነት ካልጸናበት በቀር ወረዳውን በተስፋ አያስተዳድርም፥ በእቅድና በስርዓት እንጂ! እንደው ነገሩን በስኳር ተመኻኝቶ ተነሳ እንጂ ስንት ስኳር የሆነብን ብዙ ነገር አለ፤ ያው በመጣፈጡ እንዳይደለ ልብ ይሏል። ሰላም!

 

ሊድያ ተስፋዬ

Published in መዝናኛ
Saturday, 10 February 2018 19:38

ከ«እኔ ብቻ» መሻገር

የግለኝነት መንፈስ ከሁሉም የሚከፋው እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። እንዲያም ሆኖ ዛሬ ላይ «እኔ ከሞትኩ...» ዓይነት ስሜት የሚነበብባቸውና እንዲያ ያለ ተግባር የሚታይባቸው ብዙ ሰዎች እናያለን። ለራስ ብቻ ማሰብ የስልጣኔና የመዘመን ትርጉም ውስጥ የሚካተት የሚመስለንም በርካቶች ነን። መሰልጠን ግን ሰውነትን ማክበርም ጭምር ስለሆነ ራስን ቢያስቀድሙ እንኳን ለሌሎች ሰዎች ስሜት፣ ሃሳብ፣ ሁኔታና መሰል ማሰብ እንደሚያስፈልግ ያስማማናል።
ይህን ስንል በአንድ በኩል እንደ ኢትዮጵያውያንም ነው። እኛን እኛ ያደረጉንን እሴቶችና ባህሎች ማቆየት ከፍ እንጂ ዝቅ የሚያደርገን አይደለም። ራሱን የሚወድ ሰው በቅድሚያ የሚያደርገው ነገር ራሱን ማክበር ነውና ግለኝነት በዝቶ እንኳ ቢሆን ራስን ማክበር የሚጠበቅ ጉዳይ ነው።
ወደ አለባበሳችን ልመጣ ነው ፤ ባለፈው ሳምንት በእጀ-ገባ ናሙና መረጣ (Random sampling) ሶስት ሰዎችን በሴቶች አለባበስ ዙሪያ ስላላቸው አስተያየት ጠይቀን ይዘን ቀርበን ነበር። በአንድ በኩል «እንደውም'ኮ ሴቶች እንዳሻቸው ፋሽን አልለበሱም፤ የማኅበረሰቡን ዓይን ፈርተውና በራስ መተማመን አጥተው ተቆጥበዋል» የሚል ሲኖር በሌላ በኩል ደግሞ «በልኩ ያድርጉት፤ የወንዶች ስሜት ቅርብ ነውና ራሳቸውን ለጥቃት እንዲሁም ለሀሜታ ማጋለጥ የለባቸውም» የሚሉ ሃሳቦች ተነስተው ነበር።
ዛሬ ከዛ እንቀጥል፤ ዲዛይነር ሳራ መሃመድ የኔክስት ፋሽን ዲዛይን ኮሌጅ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ናት። ስለፋሽን ምንነት እንዲህ ትላለች፤ «ፋሽን ወቅታዊ የሆነ፣ የሚያምር እንዲሁም ምቾት ያለው ነገር መገለጫ ነው። እንደየሰዉና እንደየአገሩ ሁኔታው ሊለያይ ይችላል»።
ከዚህ ባሻገር ለአለባበስ ሥርዓት እንዳለውም ነው ሳራ የምትናገረው። ልብስ ዓላማው ሰውነትን መሸፈን እስከሆነ ድረስ እንደአገሩና እንደየ አኗኗሩ ሁኔታ መሸፈን ያለበትን ሸፍኖ መንቀሳቀስ እንደሚገባም ትጠቅሳለች። በተጓዳኝ ደግሞ ለባሹ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌላውም የዓይን ምቾት መስጠት አለበት፤ ማለትም ተመልካችን መረበሽ የለበትም፤ አለባበሱም የሚያየውንም ሊያስጸይፍ የማይችል መሆን አለበት ብላለች። ይህም ሥርዓት ያለው አለባበስ መገለጫ እንደሆነ ነው የምትናገረው።
«ሥርዓት ያለው አለባበስ ይህ ነው ብሎ ለመግለጽ ይከብዳል፤ ሁሉም የመጣበት መንገድና አኗኗሩ ይወስነዋል» ያለችን ደግሞ ዲዛይነር አይዳ ታደሰ፤ የአይዲሾ ዲዛይን መስራችና ባለቤት ናት። እንደእርሷ ገለጻ ይህ ትክክል ነው ይህ ትክክል አይደለም የሚለው ነገር አይሠራም፤ ማንኛውም ሰው ራሱን አዳምጦ፣ ያለበትን አካባቢ አገናዝቦ፣ ሲለብስ ያ ትክክለኛ አለባበስ ነው ብላ እንደምታምን ትገልጻለች።
ሰዎች አንድ አለባበስ ትክክል ነው ወይም አይደለም የሚለውን አስተያየት የሚሰጡት ማኅበረሰቡ ካዘጋጀውና ከሚኖርበት ሥርዓት አንጻር፤ ደግሞ ሴቷም የዛው አካል በመሆኗ እንደሆነ ትጠቅሳለች። ሆኖም የአየር ፀባይና ቦታ የማይፈቅደው አለባበስ ትክክል አይደለም ባይ ናት። «እኛም እያደግን ነውና ያለነው የግድ የሚፈጠሩና የእኛ ባይሆኑም ከእኛ ጋር የሚዋሃዱ አልባሳት ይኖራሉ» ትላለች።
ዲዛይነር ሳራ ጋር እንመለስ፤ ከትዝብቷ ከተማ ውስጥ ብዙ አስቸጋሪ አለባበስ አለ ለማለት አትደፍርም። በአማካይ ከሁለት መቶ ሰው፤ አንድ ሰው ሥርዓት የሌለው፤ ዕድሜን የማይመጥን፣ ወቅት ያልጠበቀ ወይም ቦታን ያላማከለ አለባበስ ይለብሳል፤ እንደእርሷ አስተያየት።
በንግግሯም እንዳለችው፤ እንደዛ ለብሰው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች መጀመሪያ ለህሊናቸው ሊከብዳቸው ይገባል። ከዛ ደግሞ ተመልካችም እንዲናገራቸው እድል ስለሚከፍቱ ሰዉንም ለእላፊ ንግግር እየጋበዙ ተናጋሪ ያደርጉታል። በተለይ በከተማ ውስጥ ምቾት የማይሰጥ አለባበስ እንደሚታይ ከትዝብቷ በመነሳተ ታስረዳለች።
አንዲት ሴት ከቤቷ ስትወጣ ለምሳሌ ከመቀመጫ ወገብ ድረስ ርቅቱ አጭር የሆነ «ባትሌቱ አጭር የሆነ» ሱሪ ትለብሳለች። አለባበሷን በመስታወት ስትመለከተው ምንም የጎደለ ነገር አይታያትም። ነገር ግን በትራንስፖርት ስትንቀሳቀስ፣ ዕቃም ለማንሳት ይሁን በሌላ አጋጣሚ ስታጎነብስ ሰውነቷ ይጋለጣል። ይህም ልብሱን አመቺ አያደርገውም። በጥቅሉ፤ «በሥርዓት መልበስ ለራስ ነው የሚጠቅመው፤ ለተመልካች ማሰብ ከዛ በኋላ ነው» ትላለች ዲዛይነር ሳራ።
ወይዘሮ ትዕግስት ውህብ (ዶክተር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነልቦና ትምህርት ክፍል መምህርት ናቸው። የሴቶች አለባበስ ጉዳይ ብዙ ጊዜ ከጾታዊ ትንኮሳ ጋር እንደሚነሳ በመጥቀስ ንግግራቸውን ይጀምራሉ። «እንዴት ነው መልበስ ያለብን የሚለውን እንደሴት፤ አካባቢን ማየት፣ ባህልን፣ የት ቦታ ነው የምሄደው የሚለውንም ማገናዘብ ያስፈልጋል። ጊዜውን ከወቅቱ ጋር ማስተሳሰርና ማስተዋልም ይገባል» ይላሉ።
ከዚህ ባሻገር «ወንዱ ምን አገባው፤ ደስ ያለኝን ብለብስ» የሚል አመለካከት እንዳለ ዶክተር ትዕግስት ያነሳሉ። ለየት ያለ አለባበስ የተመልካችን ዓይን ስለሚስብ ለለከፋ ሊያጋልጥ ይችላል ይላሉም። ከዛ አልፎ ግን አለባበስ ለራስ ያለን አመለካከት ይጨምራል፤ ጥሩ ለብሶ መንቀሳቀስ ለራስ የሚሰጡትን ግምት ከፍ እንዲል ያደርጋል። ይህ ግን ለቦታውና ለጊዜው ተገቢ ሲሆን ብቻ እንደሆነ ነው የሚጠቅሱት። ያለቦታው፣ ያለጊዜው፣ ያለወቅቱና ያለሰዓቱ የሆነ አለባበስ ግን በተቃራኒው በራስ መተማመን ላይ ጫና የሚፈጥር መሆኑን ማስተዋል እንደሚገባም ያሳስባሉ።
«በተባለው መልኩ በሥርዓት ካልተለበሰ ከራስም ጋር ምቾት አይኖርም። በጣም ወጣ ያለ አለባበስ ሲለበስ መልሶ የአካባቢው ማኅበረሰብ እንዲናገረን ይሆናል፤ እነዛ አስተያየቶች ከየት መጡ ብለን ማየት አለብን። ይህም አመለካከት እኛኑ ይጎዳናል። በራስ የመተማመን ስሜትን መልሶ ሊቀንስና ሊያጠፋ ይችላል» ብለዋል።
በእርግጥም እንደተመልካች ሁላችን የምናየው ነገር አለ። ተመልካችን በሚያሳቅቅ ለባሹን ደግሞ በሚያሸማቅቅ መልኩ የለበሱት ልብስ ምኞት ሳይሰጣቸው ቀርቶ የሚጨናነቁ ሴቶች ያጋጥሙናል። ቀሚስን ወደታች መጎተት፣ ሱሪን ወደላይ ከፍ ማድረግ፣ ከላይ የተለበሰን አላባሽ ወደታች መሳብና መሰል ሁኔታዎች የሚፈጠሩት በትክክል ለለባሹ ምቾት ያልሰጠ ነገር ስላለ እንደሆነ ግልጽ ነው።
ይህን ሁሉ ይዘን ታዲያ ከዘመን አመጣሽ ፋሽን ጋር ባህልንም ሳያበላሹና ሳይጫኑ አብሮ ለማስኬድ ማስተሳሰር ይቻል እንደሆነ እንጠይቃለን። ዲዛይነር ሳራ ባህልን ከዘመናዊነት ጋር በማዋሃድ ለአገሬው ብቻ ሳይሆን በዓለም የሚታወቅ አለባበስና ጨርቅ ማምረት እንደሚቻል ትገልጻለች። የአገራችን የጥበብ ጨርቅ እንደየሄደበት አገር መስሎ እንዲታወቅና እንዲለበስ ማድረግ፤ በዓለም ተቀባይነት እንዲያገኝ በመቀላቀል መሥራት እንደሚቻል ታነሳለች።
ከዚህ አንጻር አሁን ያለንበት ጊዜ ጥሩ ነው የምትለው ሳራ፤ «በዘርፉ ብዙ የፈጠራ ባለሙያዎች ተፈጥረዋል፤ብዙ ጥበብ ያላቸው ልጆች ተወልደዋል» ብላለች። ነገር ግን የእነርሱ ድካም ብቻ ለውጥ ስለማያመጣ ሰዉ በአገሩ የተመረተ የአገሩን ልብስ መልበስን እንዲለምድ አስተሳሰብና አመለካከት መስተካከል እንዳለበት ትጠቅሳለች። ይህም ሲሆን ብቻ ባህልን ማቆየት፤ባህልን ያልጣሰ በአገር ልጅ የተሠራ ስፌትን መልበስ ይቻላል።
እናብቃ! ከልብስ መደብር ልብስ ስንገዛ ጀምሮ ስለ አለባበሳችን ልንጠነቀቅ ይገባል። ውብና ቆንጆ ሆኖ ለመታየት ከማሰብ እኩል የሌሎች ዓይን በዙሪያችን እንዳለ ልናስተውል ይገባል። በራስ መተማመናችንም ሌሎችን በመናቅና «ምን አገባቸው!» የሚል ከሆነ ይህ በራስ መተማመን ነው ለማለት ይቸግራል።
መልበስ የስልጣኔ ምልክት የሆነበት አንድ ዘመን ነበር። የሰው ልጅ ቅጠል ከመልበስ ጀምሮ ዛሬ ጨርቅን አምርቶና በተለያየ ስፌት አዘጋጅቶ ገላውን የሚሸፍንበት ዘመን ላይ ደርሰናል። የሰው ልጅ እድሜው እጅግ ሲገፋ ተመልሶ ወደልጅነት እንዲመለስ፤ የዓለም ነገርም ዕድሜዋ በሄደ ቁጥር ወደኋላ የምትራመድ ካልሆነ በቀር ዳግም እርቃን መሄድ ዛሬ ላይ ስልጣኔ ሊሆን አይችልም።
ያም ብቻ ሳይሆን፤ ከላይ እንደተነሳው ለራስ ብቻ ማሰብና «ስለሌላው ምን አገባኝ» ማለት የስልጣኔም የእኛ የኢትዮጵያውያንም መገለጫ አይደለም። «ለእኔ ከተመቸኝ...ለራሴ ነዋ...ለእኔ ይመቸኝ እንጂ» ከሚሉ እና መሰል አስተሳሰብ ሻገር ብሎ ለአካባቢ፣ ለማኅበረሰብ፣ ለባህልና ወግ ማሰብ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ወደደም ጠላ፤ በበጎም ይሁን በእኩይ ወገን ሰውን የሚሠራው በዙሪያው ያለ ማኅበረሰብ ነው፤ ያ ሰውም ራሱ በሌሎች ህይወት ውስጥ እንዲያ ያለ ሱታፌ አለው። ለዛሬው ይህን አልን፤ ህግ በኩሉስ ምን ይል ይሆን? ለቀጣይ ሳምንት ይቆየን...ሰላም!

ሊድያ ተስፋዬ

 

Published in ማህበራዊ

ኢትዮጵያ በህዝቦች መቻቻልና አብሮነት ከሚጠቀሱ አገራት መካከል ትመደባለች። በተለይም የሃይማኖት መቻቻልና አብሮ መኖር ሲነገር፤ የክርስትና እና የእስልምና ዕምነት ተከታዮች በታሪክ ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው። ህዝቡ ለሃይማኖቱ ብቻ ሳይሆን ለየሃይማኖቱ መሪዎችም ከፍተኛ ክብር የሚሰጥና ትእዛዛቸውንም የሚያከብር ነው። በዚህም የተነሳ ትልልቅ አገራዊ ጉዳዮችና ችግሮች ሲገጥሙ ህዝቡን በማስተባበሩና በማንቀሳቀሱ ረገድ የሃይማኖት መሪዎች ሲጫወቱት የነበረው ሚና ከፍተኛ ነው። 

ዛሬም አገሪቱ የጀመረችውን ጉዞ ለማፋጠን መሰረታዊ የሆኑት ሰላም፣ መከባበርና ህብረት እንዲሰፍን ከሃይማኖት አባቶች እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ብዙ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ የሰላምና የሃይማኖት መቻቻል ተምሳሌት ሆና ዘመናትን ማስቆጠር የቻለች ሀገር መሆኗን በቅርቡ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ አለም አቀፍ የሃይማኖቶች የመቻቻል ሳምንት በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ ተናግረዋል። ይሄ ከጥንት ጀምሮ የነበረ የመቻቻልና ተከባብሮ የመኖር ባህል ዛሬም ድረስ ያለና በግልፅ የሚታይ ነው። ካለፉት ሁለት አስርት አመታት ወዲህ ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁሉም ሃይማኖቶች ህገ መንግስታዊ እውቅናና ከለላ አግኝተው መንቀሳቀስ እንዲችሉ ሆነዋል።
ይህ ህገመንግስታዊ እውቅና ለሃይማኖት ተቋማት በየግላቸው ካጎናጸፋቸው መብት ባለፈ በአንድነት በመሆን ለሀገር ሰላም ልማትና ብልፅግና ብሎም ለህዝቦች አንድነት በጋራ እንዲሰሩ ሁኔታዎችንም ያመቻቸ ነው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ያሉ ሃይማኖቶች በአንድ ጉባኤ ስር ተሰባስበው መንቀሳቀስ መጀመራቸውን በማስታወስ፤ ይህም ሃይማኖቶቹ ያላቸውን የእርስ በእርስ ትስስር እንዲዳብር ከማድረግ ባሻገር፤ በአንዳንድ ቦታዎች የሚታዩ አክራሪነትና ጽንፈኝነትን ለመዋጋትም የሚያስችል ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ጠቅሰዋል።
ሁሉም ሃይማኖቶች ለሰላምና ለአንድነት መስበክ የዘወትር ተግባራቸው ሊሆን ይገባል። በተለይም በሁሉም ሃይማኖቶች አስተምህሮ የሚደገፈውን ወርቃማ ህግ (ባንተ ላይ ሊያደርጉብህ የማትፈልገውን አንተም በሌሎች ላይ አታድርግ) በማጉላትና በተከታዮቻቸው ተቀባይነት እንዲያገኝ ማድረግ፤ እንዲሁም ለሰላም፣ ለመቻቻል፣ ለሰው ልጅ ክብር መስጠት ያለውን ጠቀሜታ በማሳየት ይበልጥ ተቀባይነት እንዲኖር ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሃፊ ፓስተር ዘሪሁን ደጉ በየሃይማኖቱ የተለያዩ አስተምህሮዎች ቢኖሩም ዋናው ተልእኳቸው ለህዝብ ሰላምን መስበክና ማምጣት ነው። በአገሪቱ የሃይማኖት ተቋማትን ተሳትፎ ሲያብራሩም፤ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ላለፉት ሰባት አመታት የሀገር ውስጥ የሃይማኖት ጉባኤን በማቋቋም የሃይማኖት መቻቻልና መተማመን እንዲፈጠር ሲሰራ ቆይቷል። በኢትዮጵያ ታሪክ የነበረው ሁኔታ ሲታይ እስካሁን ችግሮች ሲከሰቱ የእምነት ተቋማትን በመጠቀም ሲፈቱና እንዳይባባሱ ይደረግ እንደነበር መመልከት እንችላለን። ዛሬም ይሄን የቀደመ መልካም ተግባር በመከተል የውስጥ ችግሮች ሲከሰቱ መፈታት ያለባቸው በሃይማኖት አባቶች በእምነት ተቋማት በኩል መሆን ይችላል ይላሉ ።
እንደፓስተር ገለጻ፤ አንድን ሰው ሰላማዊና ለሌሎች የሚያስብና የሚኖር እንዲሆን የሚያደርገው የሃይማኖት እሴት ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህን እሴቶች የየእምነቱ ሰባክያን ማስተማርና ማስፋፋት ይጠበቅባቸዋል። ከዚህም በላይ ለሰላም መታጣትና ለግጭት መነሻ የሚሆኑ በርካታ ነገሮች ቢኖሩም በአሁኑ ወቅት እንደ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ዋነኞቹ ሙስናና የመልካም አስተዳደር መጓደል እንደሆኑ ግልጽ ነው። በመሆኑም እነዚህን ለማስቆም የሃይማኖት አስተምህሮዎች ትልቅ ጠቀሜታ አላቸው።
እነዚህ ሁለት ሀገራዊ ችግሮች በየትኛውም ሃይማኖት የተወገዙና የተነቀፉ ተግባራት ናቸው። ስለዚህም የሃይማኖት አባቶችና ሰባኪያን ሃይማኖታዊ እሴቶችን በአግባቡ ማስተማርና ማስጠበቅ ከቻሉ እነዚህን ነውር የሆኑ ተግባራት መቀነስ ይቻላል። እስከ አሁን በየሃይማኖቶቹ በተሰሩ ስራዎች በርካታ ለውጦች ማምጣት ተችሏል፡፡ በመሆኑም ይሄ እሴት እንዲቀጥል ሰባኪያንና መምህራንም እውነተኛውን መንገድ ማስተማር ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የሃይማኖት አስተምህሮዎች ለተከታዮቻቸው ቅርብና እምነት የሚጣልባቸው በመሆናቸው በጥንቃቄ ካልተመሩ ለሌላ አላማ ሊውሉ የሚችሉበትም አጋጣሚ ሰፊ በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ፓስተር ዘሪሁን ይገልፃሉ። ሁሉም ሃይማኖት ሰላምን ፍቅርን ለሰው ማሰብን ይሰብካል ነገር ግን እንደ መሪዎቹና ሰባኪያኖቹ በአንዳንድ አገራት እንደሚታየው በተሳሳተ መንገድ በመተርጎም ለእኩይ ምግባር የሚውሉባቸው ሁኔታዎችም አሉ። በመሆኑም የየሃይማኖቱ መሪዎች፤ ሃይማኖትን ተንተርሶ የተሳሳተ አመለካከት በመንዛት ለሌላ አላማ የሚያውሉ ግለሰቦችን ነቅተው መጠበቅ ይገባቸዋል ሲሉ መክረዋል።
በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሰላም ግንባታ መምሪያ ሃላፊ አቶ ማሞ ወጀጋ በበኩላቸው፤ የሰላም ጉዳይ የሃይማኖት ተቋማት ዋናው የቆሙለት አላማ ነው ይላሉ። ሃላፊው እንደሚያብራሩት፤ የሃይማኖት ተቋማት ተጠሪነታቸው ለፈጣሪ እንደመሆኑ ከአምላክ የተሰጣቸው ሃላፊነት በህዝቦች መካከል ሰላምን የማወጅ፣ ሰላምን የመስበክና ሰላምን የማስተማር ሊሆን ይገባል። የሚሰሩትም ስራ በህዝቡ ዘንድ ያላቸውን ተሰሚነት በሚመጥን መልኩ መሆን አለበት። በዚህም ጊዜ ከመስመር የወጣና የህዝብ ሰላም፣ ህብረትን የሚከፋፍል ካለ እንደ መንፈሳዊ አባትነታቸው የማስተማርና የመስበክ ብቻ ሳይሆን ገስጸው የመመለስ መንፈሳዊ ስልጣንም አላቸው።
በተመሳሳይ በመንግስትም በኩል ችግር ሲኖር የሃይማኖት አባቶች እንደ ፖለቲከኞች መንግስት ስልጣን ይልቀቅ ይሄን ያድርግ የማለት ሳይሆን ማስተካከል ያለበትን ጉዳይ ለህዝብ መስራት ያለበትን ስራ እንዲሰራ በፍቅር የማስተማርና የማሳወቅ ሃላፊነት አለባቸው። በተጨማሪም አንዳንድ ጊዜ በሌሎች ሰዎች ዘንድ እንደሚታየው ስሜታዊ በሆነ መንገድ ከሚደረጉ አላስፈላጊ ተግባራትም ወጣቶችን ማስተማርና መስመር እንዲይዙ ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጡ ማስተማር ይጠበቅባቸዋል።
በኢትዮጵያ በአብዛኛው ህዝቡ የሚከተላቸው ሃይማኖቶች ክርስትናና እስልምና መሆናቸውን የጠቆሙት ሃላፊው፤ እነዚህ ሃይማኖቶች ደግሞ ከጥንት ጀምረው አብረው የኖሩ መሆናቸውን በማስታወስ ህዝቡም በሰላምና በፍቅር አብሮ ዘመናትን ማሳለፉን ተናግረዋል። በመሆኑም አሁን ካሉት የሃይማኖት ተቋማትም ሆነ መሪዎችና መምህራን የሚጠበቀው ይህን የቆየ የፍቅር የሰላም ህብረት እንዲቀጥል ማስተማርና የተግባርም አርአያ መሆን ነው ይላሉ።
ሰባኪያንን የሃይማኖት አባቶች በሃይማኖቶቹ መካከል ያለውን የፍቅር የመቻቻል ጉዞ ሲሰብኩ በህብረተሰቡ መካከል ያለውንም የመቻቻልና የአብሮነት ስሜት እያጎለበቱ መሄድ እንደሚችሉም አብራርተዋል።
ሌላው ለሰላምና ለአገር ግንባታ የሃይማኖት አባቶች መስራት ያለባቸው የነገ አገር ተረካቢ በሆነው ወጣቱ ትውልድ ላይ መሆን አለበት የሚሉት ሃላፊው፤ በፊት የነበረውና በዚህ ዘመን ያለው ወጣት እጅግ የተለያየ ሆኗል፡፡ በኢትዮጵያ እስከ 1960ዎቹ መጨረሻ ድረስ የስነምግባር ትምህርት ይሰጥ ነበር። በዛ ዘመን ያለው ወጣትና ዛሬ ያለው ወጣት ስለ ሀገርና ስለ ህዝብ ፍቅር ያለው አመለካከት አንድ አይደለም። በመሆኑም በዚህ ረገድ ከሃይማኖት ስብከት ባሻገር የቀደመው የስነ ምግባር ትምህርት እንደገና መጀመር አለበት ብለዋል።
ሃይማኖትን መስበክ ብቻ ሳይሆን ስነ ምግባርን፣ ኢትዮጵያዊነትንና አንድነትን፣ ፍቅርን በማስተማር ያለውን ሰላምና ፍቅር ማስቀጠል ይቻላል። በዚህ ጉዳይ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከዚህ ቀደም ብዙ ባይሄድበትም በማሳሰብ ደረጃ በጥያቄ መልክ ለፓርላማ አቅርቦ ነበር። አሁንም ቢሆን የሚመለከታቸው አካላት አሁን እንዳለው የስነ ዜጋ ትምህርት ሳይሆን ግብረ ገብነትን በተመለከተ ወጣቶችን ማስተማር ይጠበቃል ይላሉ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሁሉም ሃይማኖቶች የተወገዙና የአገርን አንድነትና ሰላም የሚያናጉ በዜጎች መካከል አለመተማመንን የሚፈጥሩና የሀገርን እድገትና ብልፅግና የሚያሰናክሉ ነገሮች አሉ። እነዚህም ሙስናና ወገንተኝነት ናቸው። የሁሉም ሃይማኖቶች አስተምህሮ አትስረቅ፣ አትዋሽ፣ ያንተ ያልሆነውን አትመኝ እንደሚል ይታወቃል። እነዚህን አስተምህሮዎች ክርስቲያኑም ከመጽሀፍ ቅዱስ ሙስሊሙም ከቅዱስ ቁርአን በማውጣት ማስተማርና በተከታዮቻቸው ዘንድ በማስረጽ ሙስናንና ለመቀነስና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ትልቅ ሚና መጫወት ይችላሉ ይላሉ። እነዚህን ተግባራት አለመወጣት ከፈጣሪም ከህዝብም የሚያጋጩ መሆናቸውን መስበክ እንደሚገባም ነው የገለፁት።
ሙስና እና ጎጠኝነት በአገሪቱ ቀስ በቀስ እያደጉና ስር እየሰደዱ የመጡ አገራዊ ችግሮች ናቸው። ቀደም ባሉት ዘመናት ሰው እነዚህን ነገሮች የሚያደርጋቸው ተሸማቆ ነበር፡፡ አሁን ማፈሩ ቀርቶ አደባባይ እየወጣ ነው። ይሄ ግን በአንድ ቀን ጀምበር የተከሰተ ሳይሆን በረጅም ጊዜ ሂደት ቀስ በቀስ የመጣ ነው። ችግሩን ለመቅረፍም እንደዛው ጊዜ መውስዱ አይቀርም፡፡ ዋናው ነገር ግን የሃይማኖት አስተምህሮዎችን በመጠቀም እየሸረሸሩ መቀነስ እንደሚቻል ማመኑና ማስተማሩ ላይ ነው። በተለይም ዛሬ ህጻናት የምንላቸው እና የነገ አገር ተረካቢ ወጣቶች ከዚህ አይነቱ አመለካከት የፀዱ ሆነው እንዲያድጉ ከእያንዳንዱ የሃይማኖት መሪና ሰባኪ ብዙ መስራት ይጠበቃል ይላሉ።
ሃላፊው ጨምረው እንዳብራሩት፤ የሃይማኖት አባቶችና ተቋማት አስተምህሯቸው የሆኑትን ሰላም፣ ፍቅርንና አንድነትን መስበክ ያለባቸው ደግሞ አንድ ችግር ሲከሰት ሳይሆን ዘወትር መሆን አለበት። በየእለቱ ተከታዮቻቸውን አገርን ወደሚጎዳ ህዝብን ወደ ሚያስከፋ ሰላምን ወደ ሚያሳጣ ነገር እንዳይገቡ ማስተማር አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

 

Published in ፖለቲካ

በ13 ዓመታት ውስጥ በ20/80፤ በ10/90 እና በ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራሞች 178 ሺ ቤቶች ለነዋሪ ተላልፈዋል፡፡ አሁን በ20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም 94ሺ 144 ቤት፤ 38ሺ 240 ቤት ደግሞ በ40/60 የቤት ፕሮግራም በአጠቃላይ 132ሺ 344 ቤቶች ግንባታ ላይ እንዳሉ ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

የቢሮ ሃላፊው አቶ ይድነቃቸው ዋለልኝ እንደሚናገሩት፤ ቤት መገንባት ብቻ ሳይሆን በከተማው ውስጥ ሌላ ከተማ እየተቆረቆረ ነው፡፡ ቆዬ ፈጬ ብቻውን ከ60ሺ ያላነሱ ቤቶች ተገንብተውበታል፡፡ የግንባታ አካባቢዎቹ በጣም ሰፋፊና ከፍተኛ አቅም የሚጠይቁ ናቸው፡፡
በግንባታው ሂደት ከ50ሺ በላይ ዜጎች በቋሚና በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ የ6 ወር አፈፃፀሙ ሲታይ፤ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር ተፈጥሯል፡፡ በፊት በተደጋጋሚ ይገለፅ የነበረው የፋይናንስ ችግር ተወግዷል፡፡ በግማሽ ዓመቱ ወደ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ጥቅም ላይ ውሏል፡፡
የፋይናንስ አጠቃቀሙ እንደሚያሳየው፤ በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል የተባለው የ40/60 በቁጥር17ሺ መኖሪያ ቤት አሁን 72 ነጥብ 8 በመቶ ተገንብቷል፡፡ 80 በመቶ ይጠናቀቃል የተባለው የ40/60ም 20ሺ 503 መኖሪያ ቤት 56 ነጥብ 4 በመቶ ተገንብቷል፡፡ በ20/80 የቤት ልማት በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል የተባለው 26ሺ 480 ቤት 80 በመቶ ተገንብቷል። ቀሪው 20 በመቶ በቀጣዮቹ ጊዜያት ይገነባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ይገልፃሉ፡፡
‹‹የተያዘው ሰፊ የቤት ግንባታ ሥራ በከተማ ውስጥ ያለውን መልሶ ማልማት እንዲፋጠን ለማድረግ ያለው አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም›› በማለት የተናገሩት አቶ ይድነቃቸው ቢሮው የመምህራንን አምስት ሺ ቤቶች የማደስ እና በ10/90ም ሆነ በ20/80 ቤት ማግኘት ለማይችሉ ለከተማዋ ነዋሪዎች የከተማ አስተዳደሩ የመደበውን 350 ሚሊዮን ብር ተጠቅሞ 2ሺ ቤት ማስገንባት ተጨማሪ ሥራው እንደነበር ያብራራሉ፡፡ እነዚህ ቤቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለኪራይ የሚቀርቡ መሆናቸውን አስታውሰው፤ በተቻለ አቅም ለቤት ልማት ቢሮውም ሆነ መንግስት በከፍተኛ ትኩረት እየሰሩ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ያጋጠሙ ችግሮችን አስመልክቶም አቶ ይድነቃቸው ሲገልፁ፤ በ11ኛ ዙር የተላለፉት 39ሺ 249 ቤቶች መሰረተ ልማት አልተሟላላቸውም፡፡ የ40/60ው የተሻለ ቢሆንም 20/80 ላይ እና 10/90 ላይ ቤቶች ቢተላለፉም፤ነዋሪው ገብቶ በአንዳንድ አካባቢዎች መብራትና ውሃ የለም፡፡ ኮዬ ፈጬ 9ሺ908 ቤቶች በ10/90 ተሰርተው ለነዋሪው መተላለፉ ተጠቃሚዎቹን ቢያረካውም መሰረተ ልማት ባለመሟላቱ እርካታቸው መልሶ እየጠፋ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
አቶ ይድነቃቸው እንደገለፁት፤አራብሳም 20ሺ 265 ቤት፤ ቅሊንጦ ደግሞ ሰባት ሺ አካባቢ ቤቶች መሰረተ ልማት አልተሟላላቸውም፡፡ ምንም እንኳ የአፈፃፀም ችግሩ እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ ዓመትም ቤቶች ተጠናቀው ለነዋሪዎች ማስተላለፍ ቢቻልም፤ የመሰረተ ልማት ችግር ያጋጥማል የሚል ሥጋት አለ፡፡
የቢሮ ሃላፊው እንደሚገልፁት፤ በመልካም አስተዳደር ችግርነት ተጠቅሶ በዋነኛነት ትኩረት ከተሰጡት ጉዳዮች መካከል አንደኛው ቤት መሆኑን አስታውሰው፤ፍላጎቱና አቅርቦቱ አለመመጣጠኑ የመጣበትን ምክንያት ያብራራሉ፡፡ ስለግንባታዎች መዘግየትም ይናገራሉ፡፡
ህፃዎችን ለመገንባት ከ10 እና 12 ኪሎ ሜትር ርቀት ውሃ በቦቴ እየተመላለሰ ነው፡፡ መብራት በጀነሬተር እንጂ ሃይል ማግኘት አዳጋች ነው፡፡ እነዚህ በግንባታ አፈፃፀም ላይ ሊፈጥሩ የሚችሉት ችግር ቀላል አይደለም፡፡ ሌላው የፋይናንስ ችግር ባይኖርም ተቋራጩ በሙሉ አቅሙ እየገባ አይደለም፡፡ ሁለትና ሶስት ህንፃ ይዞ አንዱን ብቻ ይሰራል፡፡ 30 ሰራተኛን ማሰማራት ሲኖርበት ሶስት ሰራተኛ ይዞ ይገነባል፡፡ የተቋራጭ አቅም ትልቅ ፈተና ሆኗል፡፡ በርካታዎች የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል ይላሉ፡፡
ሲታቀድ መጀመሪያውኑ የአቅም ግንባታ ፕሮግራም ተብሎ በመያዙ የተቋራጩን አቅም ለመገንባት ነበር፡፡ ሆኖም አሁን የአቅም ግንባታ ቆሟል፡፡ ተቋራጩ ለሰራተኛ ደመወዝ በወቅቱ አይከፍልም፡፡ አብዛኛው ተቋራጭ ዘንድ ያለው ተነሳሽነት አነስተኛ ነው፡፡ ተቋራጮቹ በቁርጥ ዋጋ ለቀን ሰራተኛ 50 እና 60 ብር እየተከፈላቸው ነው፡፡ ገበያው ግን እጥፍ ደርሷል፡፡ የእንጨትና የብረት ሰራተኛ ዋጋም ጨምሯል፡፡ ዋጋዎቹ ተገቢ አይደሉም እያሉ ነው፡፡ ይህ በጥናት መመለስ አለበት ተብሎ ተጀምሯል በማለት የተቋራጩን ጥያቄ ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ይናገራሉ፡፡አቅምን ማዕከል በማድረግ እና ቤቱ ሲተላለፍ ዋጋው እንዳይንር ሁለቱን ሚዛናዊ በማድረግ ስራው እንዲቀጥል የታሰበ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡
አቶ ይድነቃቸው የሚያነሱት ሌላው የግንባታው መጓተት መንስኤ የግብአት ትልቅ ችግር መኖሩን ነው፡፡ የውጭ ምንዛሬ እጥረት አለ፡፡ በግንባታው ላይ ላለው ብቻ 144 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በፊት ውለታ ተገብቶባቸው የነበሩ ዕቃ አቅራቢዎች ሳይቀሩ ከምንዛሬ ጭማሪው ጋር ተያይዞ የዋጋ ማሻሻያ ይደረግልን በማለት ዕቃ ማቅረባቸውን አቁመዋል፡፡ ይህም በግንባታው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል ባይ ናቸው፡፡
የመሬት ጥበት በመኖሩ ባለአራት ፎቅ ቀርቶ እስከ ሰባት ወለል እየተገነባ ይገኛል፡፡40/60 ደግሞ እስከ 18ኛ ፎቅ እየተገነባ ነው፡፡ አሳንሰር(ሊፍት) ማቅረብ ግን አልተቻለም፡፡ የአገር ውስጥ አቅም ችግር አለበት፡፡ ለተላለፉት 100 ህንፃዎች 200 አሳንሰሮች ያስፈልጓቸዋል፡፡ ነገር ግን አልተገጠመላቸውም፡፡ በቀጣይ ደግሞ 2ሺ አሳንሰር የሚያስፈልጋቸው ህንፃዎች እየተገነቡ ናቸው፡፡ ስለዚህ የውጭ ምንዛሬ ላይ ከፍተኛ ዕገዛ የሚያስፈልግ መሆኑንም ነው የሚናገሩት፡፡
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ፉፊ ድልጋሳ መጀመሪያ ከበጀት ጋር ችግር ነበር፡፡ አሁን ግን ችግሩ ተቀርፏል ይላሉ፡፡ 20 ቢሊዮን ብር ለበጀቱ ተመድቧል፡፡ ከክፍያ ጋር ተያይዞ ባንኮች ያዘገያሉ የተባለውም ተስተካክሏል፡፡መንግስት የቴክኒክ፣ የኦፕሬሽን እና አስተባባሪ ሶስት ኮሚቴ አቋቁሞ በትኩረት እየሰራ ነው በማለት በመንግስት በኩል ያለውን ተነሳሽነት ያብራራሉ፡፡
ሆኖም ግን በዛ ልክ ስራው እየተሰራ አይደለም፡፡ ህዝቡ ቆጥቧል፤ በቆጠበው ገንዘብ ተጠቃሚና ባለቤት መሆን ይፈልጋል፡፡ የ40/60ም ሆነ የ20/80 ቤቶች ችግራቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ በፊት ያጓትት የነበረው መሬቱን ነፃ የማድረግ እና የካሳ ክፍያ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
እንደአቶ ይድነቃቸው ሁሉ አቶ ፉፊም ሌላኛው ትልቁ ችግር የሥራ ተቋራጮች አቅም ማነስ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ተቋራጮችን እንዴት መደገፍና መከታተል እንደሚቻል መወያየት ያስፈልጋል፡፡ ሥራ ተቋራጮች መስፈርቱን አሟልተው ወደ ግንባታ የገቡ አይመስሉም፡፡ ለስራ የሚያስፈልጉ ባለሙያዎች፣ ማሽነሪዎችንና ተገቢውን ግብአት ይዞ ያለመግባት ችግር አለ፡፡ እንዲሁም ለግንባታ የተሰጣቸውንም ገንዘብ የሚገነቡበት አይመስሉም በማለት የተቋራጮችን ክፍተት ያስረዳሉ፡፡
ግንባታው በሚፈለገው ልክ እየተፈፀመ አይደለም፡፡ በተለይ በ2010 ይተላለፋሉ የተባሉት ቤቶች እንዲጠናቀቁ ከወዲሁ መሰራት አለበት ባይ ናቸው፡፡
የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር ዶክተር አምባቸው መኮንን፤ የሁለቱንም ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ የኢኮኖሚ አቅም በጨመረ ቁጥር ዜጎች የሚጠይቋቸው ፍላጎቶች እያደጉ ነው፡፡ በዋነኛነት የቤት ፍላጎት ሲሆን፤ ይህን ለማሳካት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ያለፉት ቤቶች ብዙ ትምህርት ተወስዶባቸዋል፡፡ በዚህ ዓመት 32 ሺ ቤቶች ይተላለፋሉ፡፡ ከሞላ ጎደል በ40/60 እና በ20/80 ይተላለፋሉ ተብለው የታሰቡት ቤቶች ብዙዎቹ ጥሩ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ ሆኖም ለውጥ ያላሳዩም ስላሉ የሚመለከታቸው አካላት መረባረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
‹‹ተቋራጮች ሥራዎችን በጥራት ጊዜውን ጠብቀው ማስረከብ አለባቸው፡፡ በሰው ሃይልም ሆነ በሥራ አመራር ብቃታቸውን ማሳደግ እና አቅማቸውን ማጎልበት ይኖርባቸዋል፡፡ ጥሩ የሥራ አመራር ብቃት እንዳላቸው ያሳዩ አሉ፡፡ በሌላ በኩል የሚጠበቅባቸውን ሥራ በጥራትና በወቅቱ መስራት ያልቻሉም አጋጥመዋል›› በማለት አንዱም የመጓተቱ ችግር የአማካሪዎችና የተቋራጮች አቅም ክፍተት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
‹‹ጊዜ ትልቅ ሀብት በመሆኑ በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል›› ያሉት ሚኒስትሩ፤ ቶሎ ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ በሌሎች አገራት እንደሚሰራው ሁሉ በርከት ያለ የሰው ሃይል ማሳተፍ፤ሌሊትም ጭምር መሰራት አለበት፡፡ የባንክ ባለሙያዎችም ቀድመው ግንባታውን ማየት አለባቸው ብለዋል፡፡
ተቋራጮቹ የተለያየ አቅምና ስነምግባር ያላቸው ናቸው፡፡ የፋይናንስ ችግር የለም፤ ስራቸውን ለሰሩ ይከፈላል፡፡ የመክፈል ሂደቱ የሚጓተት ከሆነ ይታያል፡፡ ሁሉም ሰው ተሳቆ እየሰራ ነው፡፡ማንም የማዘግየት መብት የለውም፡፡ ከዚህ ውጪ ተቋራጮችንና አማካሪዎችን የሚያቀጭጭ አሰራር ካለ መታየት እንዳለበት አያጠያይቅም ብለዋል፡፡
የግብአት አቅርቦት ችግር በሚል ለተነሳውም፤ ግንባታው ሰፊ በመሆኑ የሚያስፈልገው የብረት፣ የሲሚንቶ እና የጠጠር አቅርቦት በጣም ብዙ ነው፡፡ ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎችም አሉ፡፡ ለእነዚህ የውጭ ምንዛሬ የሚያስፈልግ በመሆኑ ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ጉዳዩ ትልቅ በመሆኑ መጓተቱን ለመቀነስ የጋራ ሥራን ይጠይቃል፡፡ ሁሉም እንደራሱ ማየት አለበት፡፡ ጉዳዩ የተወሰኑ ሰዎች ተሸክመውት የሚሰቃዩበት መሆን የለበትም በማለት ሃሳባቸውን ይደመድማሉ፡፡

 

ምህረት ሞገስ

Published in ኢኮኖሚ

በዓለም ላይ የበርካታ ቢሊዮን ዶላሮችን በኢንተርኔት አማካኝነት የሚያጭጭበረብሩ የድረገጽ በርባሪዎች በአገራት ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርሱ ቆይተዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ባሉት አባላት ቁጥር እና በሚደርሰው የዘረፋ ጉዳት አማካኝነት አደገኛ ነው የተባለለት የሳይበር ጥቃት ወንጀል ፈጻሚ ቡድን መረብን ለመበጣጠስ የሚያስችል ዘመቻ ተጀምሯል። የቡድኑ አባላትም በመላው ዓለም እየታደኑ በመታሰር ላይ መሆናቸውን የተለያዩ መገናኛ አውታሮች በመዘገብ ላይ ናቸው። 

እንደ በቢሲ ዘገባ ከሆነ፤ የአሜሪካ ፍትህ ቢሮ ብቻ በኢንተርኔት ማጭበርበር 530 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ኪሳራ አድርሷል ካለው የዓለም አቀፍ ዘረፋ በቡድን ውስጥ 13 ተጠርጣሪዎችን መያዙን አስታውቋል። ተጠርጣሪዎቹም በማረፊያ ቤት ቆይተው የኢንተርኔት ማጭበርበር ድርጊታቸው ከፍተኛ ምርመራ እየተካሄደበት ይገኛል።
በዓለም ላይ የሳይበር ጥቃት በመፈጸም ገንዘብ የሚያጭበረብረው ቡድን «ኢንፍራውድ» የተሰኘ ስም ሲኖረው፤ በተለያዩ አገራት የኮምፒውተር እውቀታቸው ከፍተኛ የሆኑ ባለሙያዎችን በአባልነት ይዟል። ከቡድኑ ውስጥ ቁልፍ ሚና ነበራቸው የተባሉ 36 ሰዎች በተለያዩ አገራት እየታደኑ በቁጥጥር ስር መዋል ጀምረዋል። የአሶሺዬትድ ፕሬስ ዘገባ ደግሞ እንደሚያመላክተው አደገኛ ቡድኑ ባለፉት ሰባት ዓመታት በቢሊዮኖች ለመዝረፍ ባደረገው ሙከራ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ መጥፎ አሻራውን ሲያሳርፍ ቆይቷል።
ከአስር ሺ በላይ አባላት ያሉት ድብቁ ቡድን የተቋቋመው በዩክሬናዊው ሲቫቶስላየ ቦነዳሬንኮ አማካኝነት ነው። መስራቹንም ሆነ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ መቀመጫውን ያደረገው አንቶኒ ናምዲ የተባለውን ሌላኛው አደገኛ ሰው በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረቶች እንደቀጠሉ ናቸው። ነገር ግን ከምስረታው ጀምሮ እጁ እንዳለበት የሚታመነው ሩሲያዊው ሰረጌይ ሜድቬዴቭ በቁጥጥር ስር ውሏል። በተጨማሪነት ከተያዙት የቡድኑ አባላት መካከል ከፈረንሳይ፣ ካናዳ፣ ፓኪስታን፣ ግብጽ፣ ጣሊያን እንዲሁም በተለያዩ አገራት መሰረታቸውን አድርገው ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ይገኙበታል። በዓለም ላይ የሚገኙ ሰዎችን የክሬዲት ካርድ መረጃ በመመዝበርም የፈለጉትን ገንዘብ ሲያጭበረብሩ እንደነበር የሚያሳዩ መረጃዎችን መርማሪዎች እያሰባሰቡ መሆናቸውም ተገልጿል።
የሳይበር ጥቃት ፈጻሚው ቡድን የገንዘብ መገበያያ ክሬዲት ካርድ ቁጥር እና የሚስጥር ቁጥሮችን በመጥለፍ የባንክ ተጠቃሚዎችን ገንዘብ ሲዘርፉ እንደነበር የተመሰረተባቸው ክስ ያመለክታል። ቡድኑም ባለፈው አመት በኢንተርኔት አማካኝነት በዓለም ላይ የሚገኙ አባሎችን ባሳተፈው ውይይት ወቅት 10 ሺ 901 አባላቱ ከየአገራቸው ሆነው ውይይቱ ላይ መሳተፋቸው ሲታወቅ ደግሞ እጁ የረዘመ አደገኛ ቡድን መሆኑን መገንዘብ ያስችላል።
ኢንፍራውድ የተሰኘው አደገኛ ቡድን የማጭበርበር ድርጊቱን ሲያከናውን የነበረው ልክ መደበኛ ንግድ እንደሚያከናውን ተቋም በዓለም ላይ በተንሰራፋው ግንኙነቱ አማካኝነት ነው የሚለውን መረጃ ያወጣው ደግሞ የአሜሪካው የህግ ቢሮ ወንጀል ጉዳዮችን የሚከታተለው ክፍል ነው።
እንደ ወንጀል ጉዳዩ ክፍል መረጃ ከሆነ፤ የቡድኑ አባላት በህገወጥ መንገድ በሸማቾች፣ በንግድ እና በፋይናንስ ተቋማት ላይ ከግማሽ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ኪሳራ አድርሰዋል። የተከሰሱትም ሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለማጭበርበር ተነሳስተዋል በሚል የወንጀል ድርጊት ነው። በሳይበር ጥቃቱ ጉዳት ከደረሰባቸው ተቋማት መካከል በዓለም ላይ ከ190 አገራት በላይ የኢንተርኔት ማገበያያ አገልግሎት የሚሰጠው ፔይፓል የተሰኘው ድርጅት እና ኢች ኤስ ቢ ሲ የተሰኘው ባንክ ይገኙበታል። በመሆኑም ቡድኑ በዓለም ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ተጨማሪ ተጠርጣሪዎችም ከተለያዩ አገራት እየታደኑ እንደሚያዙ የአሜሪካ ባለስልጣናት ዛቻ እያሰሙ ናቸው።
«በማጭበርበር እናምናለን» በሚል መፈክሩ የሚታወቀው አደገኛ ቡድኑ በዓለም ላይ የሚገኙ 4 ነጥብ ሶስት ሚሊዮን የባንክ መጠቀሚያ ካርዶችን መረጃ በመፈተሽ የብዙዎችን ኪስ ማራቆቱን ደግሞ ሬውተርስ ዘግቦታል። የኢንፍራውድ አባላት እርስ በእርስ በእውነተኛ ስማቸው እንኳን የማይተዋወቁ ቢሆንም በኢንተርኔት ግንኙነት ግን የማጭበርበር ተግባራቸው በጋራ ያከናውናሉ። ድብቁ ቡድንም ወንጀሎችን ለመፈጸም የተዋረድ ስልጣን እና አሰራርን ይከተላል። የቡድኑ አካሄድ አደገኛ በመሆኑም በአጭር ጊዜያት ውስጥ ወደ በርካታ አገራትን የመዛመት እድሉ ሰፊ ነበር። ነገር ግን አሁን የተጀመረበት መጠነ ሰፊ የምርመራ ዘመቻ ከወዲሁ አባላቶቹ እጃቸውን እንዲሰበስቡ የሚያግዝ ነው።
ቪሳ ካርድ፣ ማስተር ካርድ እና አሜሪካን ኤክስፕረስ እንዲሁም የተለያዩ ካርዶችን የሚጠቀሙ ሰዎችም የኢንተርኔት አጭበርባሪዎቹን አደገኛነት ከተረዱ በኋላ ግብይቶቻቸውን በከፍተኛ ጥንቃቄ እያከናወኑ ይገኛል። ይህም የዓለም አገራትን ኢኮኖሚ በተወሰነ መልኩ ሊጎትተው እንደሚችል የዘርፉ ተንታኞች እየገለጹ ይገኛል። የሳይበር ጥቃት ፈጻሚው ቡድን አባላት መብዛት እና ድብቅነት ሲታሰብ በአጭር ጊዜ ውስጥ መቋጫ ካልተበጀለት የዓለም አገራትን በኢኮኖሚው ሊያተራምስ የሚችል ችግር የመፍጠር አቅም እንዳለውም ተጠቁሟል።
በዓለም ላይ በቀጥታ ኢንተርኔት የሚካሄዱ የብድርና ሌሎች የፋይናንስ አገልግሎት ተግባራት የሳይበር መረጃ መዝባሪዎች እንዲሁም የኢንተርኔት ገንዘብ አጭበርባሪዎች ዋነኛ የጥቃት ኢላማ ናቸው። በዚህም በየአመቱ ከተጠቃሚዎች ላይ ያለአግባብ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የት እንደደረሰ እንኳን በውል ሳይታወቅ ደብዛው ጠፍቷል።
ስሪዬት ሜትሬክስ የተባለው የደህንነት ተቋም ባለፈው ዓመት ይፋ ባደረገው ጥናት ደግሞ ኢንተርኔት የገንዘብ ልውውጥን መሰረት አድርገው በቀጥታ የክፍያ ሥርዓት የሚያከናውኑ የፋይናንስ ድርጅቶች በሳይበር ጥቃት ፈጻሚዎች ሊደርስባቸው የሚችለው ጉዳት ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር በአንድ አመት ውስጥ 122 በመቶ ጨምሯል። ጥናቱ እንደሚያሳየው ደግሞ የወንጀል ፈጻሚዎቹ አቅም እየፈረጠመ መሆኑን ነው።
በጥናቱ ውስጥ በፋይናንስ አገልግሎት ላይ በተሰማሩ ተቋማት ላይ የተቃጡ 80 ሚሊዮን የሳይበር ጥቃቶችን መፈተሽ የተቻለ ሲሆን፤ አብዛኛዎቹ የተቋማቱን ደንበኞች መረጃ እና የሚስጥር አካውንቶችን መረጃ በመስረቅ ገንዘብ ለመዝረፍ የተደረጉ የኢንተርኔት ማጭበርበር ድርጊቶች ናቸው። የሩሲያ እና አጎራባች አገሮቿ የኮምፒውተር ባለሙያዎች፣ ከአፍሪካ እንደ ናይጀሪያ እና ግብጽ እንዲሁም የአንዳንድ የእስያ አገራት አጭበርባሪዎች በኢንተርኔት ማጭበርበሩ የተካኑ ሰዎች በብዛት የሚገኙባቸው ቦታዎች መሆናቸውንም መረጃው ያመለክታል።
እንደ ጥናቱ ከሆነ በመላው ዓለም በሚደርሰው የኢንተርኔት ዘረፋ አማካኝነት በአመት ከአስር ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የሆነ ሀብት ደብዛው ይጠፋል። የኢንተርኔት ግብይት ለአጠቃቀም ምቹ በመሆኑ እና ድካምን በመቀነስ ረገድ ተመራጭ እየሆነ በበርካታ አገራት እየተስፋፋ ቢሆንም ላልታወቁ የሳይበር ወንጀለኞች ግን ገንዘብ ማጋበሻ መንገድ መሆኑ ብዙዎችን አተርፍ ባይ አጉዳይ አድርጓቸዋል።
በመላው ዓለም ላይ የሚገኙ ግለሰቦችም ይሁኑ ተቋማት በኢንተርኔት በሚደረግ የገንዘብ ልውውጥ ላይ ጥቃት እንዳይደርስባቸው በየጊዜው የሚጠናከር የመረጃ መረብ ደህንነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ። በመሆኑም ደህንነቱ ባልተጠበቀ ድረገጽ ወይም ተቋም አማካኝነት የገንዘብ ልውውጥ የሚያከናውን በዓለም ላይ የሚገኝ ማንኛውም ሰው የኢንተርኔት ማጭበርበር እና ስርቆት ሰለባ ሊሆን ይችላል። የኢንተርኔት መረጃ ጠላፊዎች ሰለባነት የማያጋልጡ ጥብቅ አሰራሮችን እና መተግበሪያዎችን መጠቀም ያስፈልጋል። በተለይ ኢሜይል አጠቃቀም ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ባለማካሄድ የማያውቋቸው መልዕክቶች ሲላኩ በግዴለሽነት ከፍቶ መመልከቱ ለአደጋ እንደሚያጋልጥ የመረጃ ደህንነት ተቋማት ያሳስባሉ።
ያምሆነ ይህ አጭበርባሪዎቹ በየጊዜው ዕውቀታቸውን እና አቅማቸውን እያሳደጉ ስለሚሄዱ የዓለም አገራት በጋራ የጠላፊዎችን ቡድን ኔትወርክ እየተከታተሉ በመበጣጠስ ዘላቂ መፍትሄ መፈለግ እንደሚገባቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ሃሳብ ነው። ኢትዮጵያም በተለያዩ ጊዜያት በመረጃ ጠላፊዎች የምትጠቃ አገር ብትሆንም አብዛኛው ህብረተሰብ የገንዘብ ልውውጡ በኢንተርኔት ባለመሆኑ የገንዘብ ማጭበርበሩ እንደሌሎቹ የአደጉ አገራት የከፋ አይደለም። ነገር ግን ወደፊት ዓለም ወደሚሄድበት የፋይናንስ አሰራር መገባቱ የማይቀር ጉዳይ በመሆኑ ከወዲሁ የመረጃ ደህንነት ወንጀሎችን የመከላከል ልምዱ ማጠናከር በቀጣይ ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳቶችን ለመከላከል አቅም ይፈጥራል።

ጌትነት ተስፋማርያም

 

Published in ዓለም አቀፍ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።