Items filtered by date: Sunday, 11 February 2018

ባህል «ባህር» የሆነ ትርጓሜ እንዳለው የመስኩ ምሁራን ይናገራሉ። ሆኖም ቁሳዊና መንፈሳዊ ብሎ መክፈሉ ሁሉንም ያግባባል፡፡ አንድ ሕዝብ ቁሳዊና መንፈሳዊ ባህል ሊኖረው ግድ ነው፡፡ ሰው የባህሉ ፈጣሪና ውጤት ነው። ስለሆነም ባህል በሰው ይፈጠራል፤ በሰው ይከወናል። በሰው አዕምሮ የሚዘራ አዝመራ ነው፤ በሰው ልጅ አዕምሮ እየለማ፣ የሚያለማ የማህበረሰብ ፀጋ መሆኑም እሙን ነው።
ባህል የአንድ ሃገር ህዝቦች ወይም ማህበረሰቦች በጋራ የፈጠሩት ልማዳቸው፣ እምነታቸው፣ እውነታቸው፣ ስርዓታቸውን የሚያሳዩበት፣ አስተሳሰባቸውን የሚገሩበት እንዲሁም ማንነታቸውን የሚያሳውቁበት መገለጫቸው እንደሆነ ይታመናል፡፡ የማንነት መገለጫ የሆነው ዕሴት ከሌላ ዘመናዊነት ከምንለው አስተሳሰብ ጋር ብንቀይጠው ማንነትን አሳጥቶ በራሱ የማይኮራ ትውልድ እንዲበራከት ማድረጉ አይቀሬ ነው፡፡ ከዘመናዊነት ጋር የሚደባለቁትን ለይተን ብናደባልቀው የተሻለ ውጤት ማምጣቱ አይካድም፡፡ ለምሳሌ ቁሳዊ ባህላችን ከዘመናዊው ጋር ቢደባለቅ ውጤታማ ሊሆን ይችላል።
ከሩቅ ምሥራቆቹ እንደ ጃፓን፤ ከአህጉራችን ደግሞ ናይጀሪያና ደቡብ አፍሪካ ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውንና ታሪካቸውን ጠብቀው በማልማትና በማስፋፋት የተሻለ ለውጥ በማምጣት በአርአያነት ይጠቀሳሉ። ሀገራቱ የባህል ዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከፍ በማድረግ አሁን ላሉበት ደረጃ የመድረሳቸው ዋነኛ ምክንያት በአስተሳሰብና በአመለካከት መለወጥ መቻላቸው ነው።
ቀደም ሲል በሀገራችን ለባህላዊ አለባበስ፣ አመጋገብም ሆነ ባህል ነክ ለሆኑ ጉዳዮች የሚሰጠው ዋጋ እጅግ የገዘፈ ነበር። ምክንያቱም እንደዛሬው ሉላዊነት አልነገሠም፤ የባህል ወረራውም አሁን ባለው ልክ አልተስፋፋም፤ ሌሎችን የማየቱ ዕድልም እጅግ ጠባብ ነበር። አብዛኛው ሰው ለባህሉ ልዩ ፍቅር ነበረው። በመሆኑም በመጤ ባህሎች እንዲቀየጥበት አይፈቅድም፤ እራሱም አይቀይጥም።
ስልጣኔ በባህላችን ላይ ያሳደረው ጫና ብዙ ነው፤ በልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎችና የግንኙነት መስተጋብራችን ውስጥ ሥልጣኔ ስቦ ያመጣውን ጫና አዎንታዊውን ከአሉታዊ መለየት ይገባል። ካለው መልካም ባህል፤ አገራዊ ወግና ልማድ ጋር በተጣጣመ መልኩ ተያይዞ እንዲሄድ ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነትም ግዴትም ነው።
ኢትዮጵያ በተለያዩ ባህሎች የታደለች አገር ናት። ህዝቦቿ ለዘመናት ሲለማመዱት የቆዩትና የራሳቸው ያደረጉት ቱባ ባህል አላቸው። በዚህ ባህል ውስጥ ኖሯል፣ አልፏል ለልጆቹም አውርሷል፡፡ ተረካቢዎቹ ትውልዶችም በዘመን ሂደት እያሻሻሉ፤ በጎደለ እየሞሉ ጠብቀው አቆይተውታል። እንኳን ባህልን ማስጎብኘት የገቢ ምንጭ በሆነበት ዘመን ላይ ተገኝተን ይቅርና ባህል የዓለም ውበት በመሆኑ ብቻ የማይነጥፍ ሀብት ሆኗል። ለዚህም ነው መጠበቅ፣ መንከባከብ፣ ማስረከብና የተሻለውን ለማቆየት የባህሉ ባለቤቶች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው መባሉ።
በአሁኑ ወቅት ባህላችን እየተሸረሸረ ለመምጣቱ ጥናት ማቅረብ አይጠበቅም፡፡ ምክንያቱም የምናያቸውና የምንሰማቸው እውነታዎች በቂ ማስረጃዎች ናቸውና። አዲሱ ትውልድ ሙሉ ለሙሉ ባህሉን ረስቷል ባይባልም፤ የቀድሞውን ትውልድ ያህል ግንዛቤ አለው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ይህ የባህል ወረራ ለአገር ተረካቢው ትውልድ ስጋት መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡
ባህልን ማክበርና መጠበቅ ከቤት ይጀምራል፡፡ ባህልን በመጠበቅና ከብረዛ ለመከላከል ወላጆችና የትምህርት ተቋማት ከፍተኛውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል፡፡ ባህልን የመጠበቅ ሥራ ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ሁላችንም በንቃት ልንሳተፍ ግድ ይለናል።
በመንግሥት ደረጃ ባህልን ከብረዛ ለመከላከልና ለማልማት የሚያስችል የባህል ፖሊሲ ወጥቶ በሥራ ላይ ይገኛል። ይሁን እንጅ ስለ ፖሊሲው ምንነት የሚያውቀው ማህበረሰብ በቂ ነው ለማለት አያስደፍርም። ግንዛቤው ሳይፈጠርና ሳይታወቅ ደግሞ ወደ ተግባር መግባት አይቻልም። ስለዚህ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት ባለመሆኑ ፖሊሲውን ያወጣውን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን ጨምሮ በጉዳዩ ላይ የሚሠሩ ባለድርሻ አካላት ሊያስቡበት ይገባል። ሰፊ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ በተከታታይነት ሊሠራ ይገባል፡፡ የባህል ወረራ በወረቀት ላይ በሰፈረ ፖሊሲ ብቻ የሚቆም አይደለም። በመሆኑም ፖሊሲውን በመተግባርና በማስተግበር ረገድ ብዙ ርቀት መጓዝ ይገባል።
የባህል ወረራን ለማስቀረት መጀመሪያ የራስን ባህል ማወቅና ማሳወቅ የግድ ይላል። የባህል ፖሊሲው የራሱ ግዴታዎችና አፈፃፀሞችን በዝርዝር ለማህበረሰቡ ማስረዳትም ይገባል። በፖሊሲው ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተሠራ ቢሆንም ፖሊሲው ከወጣ ጀምሮ ምን ለውጦች አምጥቷል? ቢባል ያን ያህል የገዘፈ መልስ ሊገኝ አይችልም። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የባህል ወረራው እየበዛ እንጂ እየቀሰነ አይደለም። የባህል ፖሊሲውን ሊያስተገብር የሚችለው የመጀመሪያው አካል ራሱ ማህበረሰቡ በመሆኑ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል።
የባህል ፖሊሲ መቅረጽ ብቻ በራሱ ግብ አይደለም፡፡ ለተግባራዊነቱ መትጋት ይገባል። ሥራው የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በመሆኑ ርብርቡ መጠናከር አለበት። የውጭ ናፋቂ ከመሆን አስቀድሞ የራስን ባህልና የባህል ፖሊሲውን ማወቅና ማስተዋወቅ ላይ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል። ባህል በሃሳብና በልብ የሚሰርፅ እውነታም ጭምር ነው። የሌላን ናፋቂ ትውልድ ለአገሩ የማይጠቅም፤ በተበረዘ ባህል የሚናውዝና ማንነቱን የሚክድ ትውልድም መበራከት የለበትም። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ትውልዱን ከባህል ወረራ መታደግ የሚቻለው።

Published in ርዕሰ አንቀፅ
Sunday, 11 February 2018 00:49

ስታዲየሙ ዝም ሲል

ዛሬ ስለ እግር ኳስ እንፅፋለን። ስንፅፍ ግን አሁን ከሚታየው እና በመረጃ ብዛት ናላን ከሚያዞረው የወቅቱ ፋሽን ገለል ብለን ነው። ይህን ስንል የሁሉም ቀልብ የሚያርፍበትን «ክቧን ኳስ» በተለየ የታሪክ እና የግል ምልከታ ላይ በማተኮር ሚስጥሯን ለማወቅ እንታትራለን ማለት ነው። ይህን ማግኘት የምንችለው ደግሞ የግዴታ አሁን በእግር ኳሱ ላይ ያለውን ፋሽን ወደኋላ ተወት አድርገን ባልተሄደበት መንገድ መጓዝ ስንችል እንደሆነ እናምናለን። መቼም ሳናምን አንፅፍም!
ምስጢር -1
በሆነ አጋጣሚ በአንድ ባዶ የእግር ኳስ ስታዲየም ውስጥ ተገኝታችሁ ታውቃላችሁ? ይህን አጋጣሚ ካላገኛችሁ ለማግኘት ሞክሩ። በስታዲየሙ ውስጥ እንደገባችሁ ቀጥታ ወደ መሀል ሜዳው ሂዱና ለትንሽ ደቂቃ ዝም ብላችሁ ቁሙ። እኔ እላችኋለሁ፤ ከዚህ በፊት ፀጥ ያለ አካባቢ አጋጥሟችሁ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ልክ በዚያ ስታዲየም ውስጥ እንዳለ ፀጥታ ሌላ የትም ሊኖር እንደማይችል በቦታው ስትሆኑ ትገነዘባላችሁ። ባዶነት እራሱ በስታዲየሙ ውስጥ ባዶ ይሆናል። ይህ የሚሆነው ግን ፍፁም ከእግር ኳስ የራቃችሁ እና በስታዲየሙ ውስጥ ቅንጣትም ትውስታ የሌላችሁ ከሆነ ብቻ ነው።
እስቲ ወደኋላ መለስ ብለን ታሪክ የሚያስታ ውሳቸውን ስታዲየሞች ሰው በተሞላባቸው ጊዜያቶች የደስታ ሲቃ እና የጠለቀ የሀዘን ስሜት ሲያስተናግዱ እንመልከት። ይህን ስንል ዶሴው እንድናስታውስ የሚያስገድደን የ1966ቱን የዓለም ዋንጫ ነው። የዌምብሌ ስታዲየም ተጉዛችሁ ብቻችሁን ስታዲየሙ ውስጥ ብትታደሙ የእግር ኳስ ፈጣሪዎቹን ድል በደጋፊዎቹ አስረሽ ምቺው እስካሁንም ድረስ ሲያስተጋባ ታደምጣላችሁ። ምዕራብ ጀርመንን በመርታት የድል ፅዋውን ከፍ ያደረገችው እንግሊዝ እና ዜጎቿ ደግሞ ሌላ የአለም ዋንጫ ድል እስካላጣጣሙ ድረስ በዚህ ስታዲየም ሲገኙ ይህ ድምፅ ያቃጭልባቸዋል። ሁልጊዜም የማይረሱት እና የሚያጣጥር የሲቃ ድምፅ የሚሆንባቸው ደግሞ የ1953 የሀንጋሪ የ6ለ3 ሽንፈት ነው።
60 አመታትን ወደኋላ መለስ ስንል የምንመለከተው ዌምብለይ ስታዲየም የአለም ዋንጫን ከማንሳት በላይ እንደ እሾህ የሚቆጠቁጥ ሽንፈት እንዳስተናገደ ነው። ድል ብቻ ሳይሆን መረታት በሜዳው ውስጥ እኔ እብስ እኔ እብስ እያሉ ሲሽቀዳደሙ ከጫጫታም በላይ የሆነ ግርታ በአይምሯችሁ ውስጥ ይከሰታል።
አሁንም እዛው ስታዲየም ውስጥ ነን ። ነገር ግን በሌላ ሰፍራ የሚገኝ የእግር ኳስ ቤት። ብራዚል ማራካኛ ስታዲየም እንገኛለን። ይህ ወቅት ለብራዚላዊያን፤ ሊያውም እግር ኳስን በቅንጦት ለሚጫወቷት ደቡብ አሜሪካውያን እንደ ዱብዳ የሚቆጠር ጊዜ ነው። በቡድን ድልድል ውስጥ የነጥብ ብልጫ ያለው ብቻ የአለም ዋንጫውን በሚያነሳበት የጊዜው ውድድር፤ ለፍፃሜው ከኡራጋይ ጋር የገጠመችው ብራዚል ብልጫ ወስዳ ድልን ለመጎናፀፍ አለመሸነፍ ብቻ ይበቃት ነበር። ይህ አልሆነም። በባላጋራዋ የ2ለ1 ሽንፈት ተከናነበች። የምትጓጓለትን ዋንጫ በግዳጅ ተነጠቀች።
ብራዚላውያን በሌሎች የአለም ዋንጫ ድሎች ቁስላቸው ቢሽርላቸውም የማራካኛ ስታዲየም ግን እስካሁንም ድረስ በዝምታ ውስጥ የሀዘን እንጉርጉሮን ያዜማሉ። ዝም ሲል ብሶት ይተናነቃቸዋል። በአርጀንቲናም ይሄ ታሪክ ያው ነው። በቦነስ አይረስ የሚገኘው ባለ አራት መአዘኑ የቦምቦኔራ ስታዲየም የድል እና ሽንፈት ከበሮ ሲደለቅበት ግማሽ ክፍለ ዘመን አለፈው። በዚህ ጉዳይ ላይ የሜክሲኮው አዝካ ስታዲየም ተመሳሳይ ድምፅ ያስተጋባል። በባህላዊው የአገሬው ሚጥሚጣ እንደመለብለብ አይነት ሀዘን። ደግሞም በድል ቃጠሎውን እንደማጥፋት። ይህ ሁሉ ግን በዝምታው ውስጥ ብቻ የሚደመጥ ድምፅ ነው።
ወደ ጣሊያኗ ሚላን ልውሰዳችሁ። ጊውሴፔ ሜዛ ስታዲዮም። እግር ኳስን ተጫውተው ያለፉ ጥበበኛ መንፈሶች ምሽት ምሽት ኳስን ከመረብ እንደሚያገናኙበት አንዳች ነገር ስታዲዮሙን ስታዩ ይነግራችኋል። ዳኛው የተሰራውን ጥፋት ለማስቆም «ፊሽካውን» እንደሚያፈነዳበት ጥርጥር የለውም። ይሄ ስታዲየም ዝም ቢል እንኳን ዝም አይልም። ምክንያቱም ብዙ የፈንጠዝያ እና ቅስም የሚሰብር የእግር ኳስ ክስተቶችን አስተናግዷል። እያንዳንዱ የስታዲየሙ ጥጋት ዘመን የሚያስታውሰው ታሪክ አለው። በዚህኛው ጎን ከመቀመጫ ብድግ የሚያስብል አስደናቂ ጎል ተመልካቹ ሲያይ፤ በሌላኛው ጎን ደግሞ እጅን አፍ ላይ አስጭኖ አይን የሚያስፈጥጥ መሳት የሌለበት ግብ ተቆጥሯል።
ታዲያ ይሄን ሁሉ ታሪክ ተሸክሞ የሳን ሴሮው ስታዲየም እንዴት ዝም ሊል ይችላል። ቢያንስ ቢያንስ አፍ አውጥቶ ባይናገር በጥሞና ለተመለከተው ሁሉ አንዳች የሚከብድ መንፈስ አንደረበበበት በሚስጥር ያሳብቃል እንጂ። አሊያማ ከሳውዳረቢያው ከ«ኪንግ ፉዓድ» ስታዲየም ምን ይለየዋል። በበረሀ መሀል እንዳለው። ከበረሀው በላይ በረሀ እንደሆነው። የተመልካች ድርቅ በየጊዜው እንደሚመታው። በዚህ ስታዲየም ውስጥ ኳስ ማንከባለል ቅሪላ ከመግፋት አይተናነስም። ኳስ ያለ ተመልካች እንዲህ ውበቷን ታጣለች እንዴ? ኳስ ያለ የሚያስገመግም የድጋፍ ድምፅ እና ቁጣ ብቻዋን የምታወጣው ድምፅ ከመደበርም በላይ ይቀፋል። እንደገና ደግሞ ምንም ታሪክ ያልተሰራበት ባዶ ስታዲየም ከውሃ ማጠራቀሚያ ጋን የተለየ ቁስ አለመሆኑን ነገርየውን ልብ ብሎ ለታዘበው በቂ ግንዛቤን ያገኝበታል። ከኪንግ ፋዓድ ስታዲየም ውጪ የዘረዘርናቸው ሜዳዎች ግን ድቡልቡሏ የእግር ኳስ ከፀሀይ እና ከጨረቃ እኩል ገዝፋ እንድትታይ ውበት ደርበውላታል።
ሁልጊዜም ቢሆን እነዚህ ስታዲየሞቹ ጨዋታዎችን ሲያስተናግዱ በባለሜዳው ደጋፊዎች ያሸበርቃሉ። ልክ እንደ ንጉስ ቤተ መንግስት «ካስትል» ግርማ ሞገሳቸው በእጥፍ ይጨምራል። ባላንጣዎች ጥቂት ስፍራ ይፈቀድላቸዋል። ሆኖም ድምፃቸው ካሉበት ቦታ ግዘፎ ነስቶ መላው ስታዲየም ውስጥ ይንሰራፋል። ነጩ የሜዳ መስመር ሁለቱን ባላጋራዎች ጨዋታው እስኪጀመር እንደ ድንበር ይለያቸዋል። ሁል ጊዜም በግራና በቀኝ ያሉት የግብ አግዳሚዎች ጀርባ ያሉ ደጋፊዎች የሚቀመጡባቸው ቦታዎች የአደጋ ቀጣና ይባላሉ «danger zone» በደጋፊዎቹ ጩኸት በረኛች እጃቸው ኳስን ከመያዝ ትቦዝናለች። አጥቂዎች እግራቸው ቄጤማ ይሆናል። የበረታ የድል ፅዋውን ሲጎነጭ፤ ሌላኛው መሪር ሽንፈትን ይከናነባል። አንገት ለአንገት የተናነቁት ተከባብረው በእኩል ውጤት ይለያያሉ። ስታዲየሞች ያኔ ነው ከባዶነት ተነስተው ታሪክ መሸከም የሚጀምሩት።
ምስጢር -2
እግር ኳስ ከሰላማዊ ጦርነት የዘለለ አጋጣሚን ያስተናግዳል። መጫወት ከመሸናነፍ ጋር ሲደበላለቅ የክብር ጉዳይ ይመጣል። ድንገት መሀል ሜዳ ላይ ግጭት ይፈጠራል። ደጋፊዎች በወንበር ይፈነካከታሉ። ከጨዋታው በኋላ በሚፈጠር ግጭት በሜዳ ውስጥ እና ከሜዳ ውጪ የሰው ልጅ ህይወት ይቀጠፋል። ኳስ ድምፅ፣ ትንፋሽ፣ ጉልበት ብቻ ሳይሆን ደም ይከፈልባታል። እግር እንክት ብሎ እስከወዲያኛው ላይመለስ ይሰናበታል። ልብ መሮጥ ደክሟት መሀል ሜዳ ላይ ቀጥ ብላ እስከወዲያኛው አለምን ትሰናበታለች። አለም ላይ ግጭትን ያስነሳሉ ተብለው እሹሩሩ ከሚባሉት ሀይማኖት እና ፖለቲካ ባልተናነሰ በእግር ኳስ ጨዋታ ብቻ ስፍራዎች የጦርነት አውድማ ይሆናሉ። አንዳንዶች እንዲያውም ጠንከር ያለ ብያኔ ሲሰጡ «በእግር ኳስ ግጭትና ጥላቻ አይፈጠርም ማለት መሀረብ እንባን አይጠርግም ብሎ እንደመከራከር ነው» በማለት ይደመድማሉ።
እስቲ ይሄን ጉዳይ ጠንከር አድርጎ ወደሚያስረዳን እንድ ታሪክ እንመለስ። ጊዜው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1969 ነበር። ሁንዱራስ እና ኤል ሳልቫዶር በሚባሉ ሁለት በጣም ደሀና ሚጢጢዬ የመካከለኛው አሜሪካ አገራት ቅልጥ ያለ ጦርነት
ተነሳ።

ዳግም ከበደ

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ አምራች ፋብሪካዎች አቅም በመቀነሱ ምክንያት የዘርፉ የወጪ ንግድ ባለፉት ስድስት ወራት መቀነሱን የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የንግድ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ አምራች ፋብሪካዎች ከግብዓት እጥረት ጋር በተያያዘ በተፈጠረባቸው የአቅም ማነስ ምክንያት ምርቶችን በብዛት ወደ ውጭ መላክ አልቻሉም። ይህ ደግሞ የሚመለከ ታቸው የመንግሥት አካላት እና ድርጅቶቹ ችግሮቹን በጋራ መቀነስ እንዳለባቸው የሚያመላክት ነው። ስለዚህም በበጀት ዓመቱ ቀሪ ጊዜያት በጥራት እና በብዛታቸው ተመራጭ የሆኑ ምርቶች እንዲላኩ ጥረት ማድረግ ይገባል።
በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የጨርቃጨርቅና አልባሳት ምርቶች 89 ነጥብ 57 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንዲያስገቡ ታቅዶላቸው ነበር። ነገር ግን አፈጻጸሙ 52 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ነው። ይህ ደግሞ ከአምናው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ24 ነጥብ 9 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ከተያዘለት እቅድ ጋር ሲነጻጸር ግን 58 በመቶ ብቻ መሆኑ ከግንዛቤ ውስጥ ሲገባ ዘርፉ ዝቅተኛ አፈጻጸም ላይ እንዳለ ነው አቶ ወንድሙ የተናገሩት።
እንደ አቶ ወንድሙ ገለጻ፤ ለዕቅድ አፈፃፀሙ ጉድለት የሚጠቀሱ ዋና ዋና ምክንያቶች በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የኤክስፖርት ገቢ ዕቅድ 80 በመቶ ድርሻ ከነበራቸው ድርጅቶች ውስጥ አብዛኛዎቹ ወደ ውጭ እንዲልኩ ከሚጠበቁት ምርቶች ከግማሽ በታች መላካቸው ነው። በተለይ የዘርፉን ወጪ ንግድ በማሳደግ ረገድ ከፍተኛውን አስተዋፅኦ የሚያደርገው አይካ አዲስ ቴክስታይል በመሆኑ ካለፉት አራት ወራት ጀምሮ ከተለያዩ የጨርቃጨርቅ ምርቶች ግብዓት ጋር ተያይዞ እጥረት ስለገጠመው የገበያ ትዕዛዞቹን በወቅቱ ማድረስ አልቻለም። ይህም በወጪ ንግዱ መቀዛቀዝ እና በድርጅቱ ገቢ መቀነስ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ከፍተኛ እንዲሆን አድርጓል። በመሆኑም በመንግሥት እና በተቋሙ በኩል ለችግሩ መፍትሄ ለማበጀት ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

ጌትነት ተስፋማርያም

Published in የሀገር ውስጥ

አዲስ አበባ፡- ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተደረገውን የውጭ ምንዛሬ ለውጥ ተከትሎ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ የንግድ ድርጅቶች ላይ የተጀመረው የክስ ሂደት እና ማጣራት መቀጠሉን የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

በኢፌዴሪ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን የበጀት ዳይሬክተር አቶ አማረ ወልዱ እንደገለጹት፤ በምንዛሪ ለውጥ ምክንያት ያለአግባብ ህብረተሰቡ ላይ ዋጋ የጨመሩ እና ምርት በመደበቅ ተግባር የተጠረጠሩ የንግድ ድርጅቶች ላይ የማጣራት ሂደቱ ቀጥሏል። ባለፉት ስድስት ወራት በተከናወነው ሥራም 214 የንግድ ተቋማት ላይ ማጣራት ተደርጎ 62 የንግድ ድርጅቶች ላይ ክስ ተመስርቷል። በተጨማሪም 42 የንግድ ሱቆች እንዲታሸጉ የተደረገ ሲሆን፤ የዋጋ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ማስጠነቀቂያ የተሰጣቸው አሉ። በቀጣይም ተገቢውን የህግ ቅጣት የሚሰጣቸው የንግድ ድርጅቶች የሚኖሩ ሲሆን፤ የ119ኙ ጉዳይ ደግሞ በክርክር ሂደት ላይ ይገኛል።
እንደ አቶ አማረ ገለጻ፤ ባለስልጣኑ ሰፊ የማጣራት እና የክስ ሂደቶችን እንዳያከናውን የሰው ኃይል እጥረት እንቅፋት ሆኖበታል። የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ ለመወጣት እንዳይችል በማድረግ ህገወጥ ንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚያደርገውን ክትትል አቅም እንዲቀንስ እያደረገው ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በጻፉት ደብዳቤ መሰረት ከዓቃቤ ህግ እና ከፖሊስ አካላት ለክስ እና ምርመራ ሂደቶች የሚያግዙ 30 ሰዎች ለባለስልጣኑ እንዲመደቡ የተላለፈው ውሳኔ ተፈጻሚ አልሆነም። በዚህም ክትትሉን እና የክስ ሂደቶችን በስፋት እንዳያከናውን ችግር መፍጠሩን ጠቁመዋል።
በንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የኮርፖሬት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግርማ አለማር በበኩላቸው፤ ባለፉት ወራት መንግሥት የ15 በመቶ የብር የመግዛት አቅም መቀነሱን ተከትሎ የግል ጥቅማቸውን ለማካበት የሚፈልጉ ነጋዴዎች የዋጋ ጨማሪ ሲያደርጉ ተይዘዋል። በእንስሳት መድኃኒት አቅርቦት ላይ ከ2 ነጥብ 8 በመቶ እስከ 140 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ነጋዴዎች ተገኝተዋል። የንግድ ሂደቱን የተረጋጋ ለማድረግ ባለስልጣኑ ባለው የሰው ኃይል ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በተለያዩ ዘርፎች ላይ ያለአግባብ ጭማሪ ያደረጉ ድርጅቶች መኖራ ቸውን የሚጠቁሙት አቶ ግርማ፤ በተለይ በብረት ንግድ ላይ ከ50 በመቶ በላይ ጭማሪ ያደረጉ ነጋዴዎች ምክንያታቸው አሳማኝ እንዳልነበረ አስታውሰዋል።
አብዛኛው የብረት ምርት ወጪ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ሲሆን፤ ፍጆታው ግን በኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ጭማሪ ባለማሳየቱ የነጋዴዎቹ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ምክንያታዊ ባለመሆኑ ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል። በብረት ንግድ ላይ ከተሰማሩት መካከል 50 የሚደርሱት ላይ ምርመራ የተደ ረገባቸው ሲሆን፤ ችግር በተስተ ዋለባቸው 16 ድርጅቶች ላይ ክስ መመስረቱን ገልጸዋል። በተመሳሳይ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚደረገው ማጣራት እና የክስ ሂደት እንደ ሚጠናከር ጠቁመዋል።

 

ጌትነት ተስፋማርያም

Published in የሀገር ውስጥ

አንዳንዶች «እንቅፋት!» በሚል ስም ይጠሯቸዋል። ሰዎች ወደቤታቸው ሲያቀኑ በመንገዳቸው የሚያጋጥሟቸውን መሸታ ቤቶች። እነዚህ እንቅፋቶች ወደቤቱ ለመሄድ መንገድ ላይ ያለን ሰው ብቻ ሳይሆን ትውልድን ወደነገ የሚያደርገውን ጉዞ ሲያደናቅፉ ይስተዋላል። መዲናዪቱም በመጤ ባህሎች በመወረር እንዲህ ያለው እንቅፋት የበዛባት ከተማ ከሆነች ሰነባብታለች። ይህም በአብዛኛው ህብረተሰብ ዘንድ ጉዳዩ የሚመለከተው አካል የሌለ አልያም ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ የተከናነበ ያህል ስሜት እየፈጠረ ይገኛል።

በሌላ ወገን መጤ ባህልን ለመከላከልና የነበረውን በጎ ባህል ለማዳበር እንቀሳቀሳለሁ የሚል «ባለድርሻ» አካል አለሁ ሲል ይሰማል። ይህም ሆኖ ግን እነዚህ እንቅፋት የሚባሉ ጭፈራ ቤቶች፣ መጠጥ ቤቶች፣ የራቁት ዳንስና ሺሻ ማስጨሻዎች፣ ጫት ማስቃሚያ እንዲሁም መሰል መጤ ባህል የሚጎበኛቸው ቤቶች ግዛታቸውን እያስፋፉ፤ አሠራራቸውም እየዘመነ ሄዷል። የንግድ ኃላፊዎችም በአንድ ጎን ለቤቶቹ ፈቃድ ሰጪዎች ራሳቸው ሆነው ይገኛሉ። «ሰ'ዶ ማሳደድ...» እንዲሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ወርቁ መንገሻ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በቢሮ ደረጃ ከተዋቀረ አስር ዓመታት እንደተቆጠሩ ያስታውሳሉ። መዋቅሩንም እስከወረዳ ድረስ አስፍቷል። «መዋቅሩ መዘርጋቱ ትልቅ እፎይታን ሰጥቶናል፤ ይህ የተደረገው ከባህል ጋር ተያያዥ የሆነ ሥራ መሥራት የሚቻለው ታች ያለው ህብረተሰብ ጋር በመሆኑ ነው» ይላሉ።
መዋቅሩ ከተዘረጋና ሥራ ከተጀመረ በኋላ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በማስቀረት፣ የገንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በመሥራት፣ በመገናኛ ብዙኀን በኩል መረጃዎችን በማቀበል ጥሩ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ። ይሁን እንጅ በተለይ መጤ ባህልን በሚመለከት ካለው ስጋት አንጻር የተሠራው በቂ እንዳልሆነ ይናገራሉ።
ችግሩን በመከላከል ረገድ አንድ ዕርምጃ ወደፊት ያስሄዳል የተባለለት ምክር ቤትም ከሦስት ዓመታት በፊት መቋቋሙን ይጠቁማሉ። ምክር ቤቱም በከተማ ደረጃ በከንቲባው የሚመራ ሆኖ ታች የክፍለ ከተማ እና የወረዳ የባህልና ቱሪዝም ጽሕፈትቤቶች ብቻቸውን ማምጣት ያልቻሉትን ለውጥ ከሌሎች ክፍሎች ጋር በጋራ ለማምጣት ያለመ ነው።
አቶ ወርቁ እንዳሉት፤ ይህ አሠራር «እኔን አይመለከተኝም» የሚል ክፍል እንዳይኖር ያግዛል። በዚህም አዲስ መዋቅር ከፖሊስ፣ ንግድና ኢንዱስትሪ፣ ሴቶችና ሕፃናት፣ ከትምህርት ቢሮ፣ መድኃኒትና ምግብ ቁጥጥር ባለሥልጣንና ሌሎችም አካላት ጋር አብረን እንሠራለን ተባብለዋል። ይህም ሆኖ ግን ቅንጅቱ በራሱ ጅማሮ እንደሆነና ብዙ የሚጠበቅ ሥራ እንዳለ ይገልጻሉ።
የአልባሌ ቦታዎቹን ጉዳት በመከላከል ረገድ ቦሌ ክፍለከተማ በቀዳሚነት ተጠቃሽ መሆኑን የሚያሳዩ ጥናቶች እንዳሉ የሚናገሩት ደግሞ በቦሌ ክፍለ ከተማ የባህል እሴቶች ኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪ አቶ ዳዊት አፈወርቅ ናቸው። ችግሩን ለመከላከል በክፍለከተማው በሚገኙ 15 ወረዳዎች ለወጣቶች ጊዜ ማሳለፊያና መሰብሰቢያ የስነጽሑፍ ምሽቶችን ማዘጋጀትና የኪነጥበብ ቡድኖች መፍጠርን እንደአማራጭ ተወስደዋል።
ለጉዳዩ መፍትሔ ለመስጠትም በየወረዳው ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ መሆኑን ይናገራሉ። መጠጥና ጭፈራ ቤቶች በብዛት የሚታዩባቸው አካባቢዎች እንደታወቁም ይጠቅሳሉ። «ልንቆጣጠረው ያልቻልነው ሰፊ ችግር አለ» የሚሉት አቶ ዳዊት፤ በባርና ሬስቶራንት ወይም በማሳጅ ቤት ስም የሚከፈቱ ቤቶችን በሚመለከት፤ የንግድ ፈቃድ ለመስጠት ወይም ፈቃድ ለማደስ በሚደረግ ቅኝት ቤቶቹ ከትምህርት ቤት ምን ያህል እንደሚርቁና የድምፅ ብክለት መኖር አለመኖሩን በዋናነት የሚታይ መሆኑን ይናገራሉ።
እንዲያም ሆኖ የተጠቀሱት ጉዳዮች በትክክል የተቃኙ ባይመስሉም የወጣቱ የህይወት መንገድ በአጓጉል ሱስ ተጠምዶ መባከኑን በሚያገናዝብ መልኩ የሚሠራ ሥራ በባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት በኩል እንደሌለ ከአቶ ዳዊት ንግግር መረዳት ይቻላል። ቡድን መሪው ለዚህ ችግር ብለው የጠቀሱት ታች እስከወረዳ ድረስ በእኔነት ስሜት ሳይሆን ኃላፊነቱ ጥቅም ያስገኝ ይመስል «ሥልጣኑ ለእኔ ይሰጠኝ» ሽኩቻ መሆኑን ያነሳሉ። በዚህም አንዱ ያሸገውን የንግድ ቤት ሌላው በገዛ ሥልጣኑ ሲከፍት ማስተዋላቸውን ያስረዳሉ።
ወይዘሮ ሲቲና ሲራጅ በአራዳ ክፍለ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊት ናቸው። በክፍለከተማቸው መጤ ባህልን ለመከላከል አስወጋጅ ኮሚቴ ተዋቅሯል። ይህም በየወረዳው በምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሚመራ መሆኑንና የተቋቋመውም በያዝነው ዓመት መሆኑን ይገልጻሉ። ይህም ኮሚቴ በተለይ ከደንብ ማስከበር፣ ከፖሊስና ከሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ጋር በመሆን ወደሥራ ለመግባት ቅድመ ዝግጅት ላይ ነው።
«መጤ ባህልን የሚጋብዙ ንግድ ቤቶችን ላይ እርምጃ ከመወሰዱ በፊት ራሳቸው ድርጅቶቹ አምነውበት እንዲዘጉና ወደሌላ ሥራ እንዲቀይሩ ምክክር ይደረጋል። ከደንብ አስከባሪዎች ጋር በመተባበር እንዲዘጉ የተደረጉ ቤቶችም አሉ።» በማለት አስታውሰው፤ በዋናነት ግን ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንደሚያስቀ ድሙም ጠቁመዋል።
በክፍለ ከተማው እንደሌሎቹ ሁሉ መጤ ባህልን ለመከላከል ኮሚቴ የተቋቋመ መሆኑን የሚጠቅሱት የአቃቂ ክፍለከተማ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳዊት ወልደሚካኤል ናቸው። እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ባለፈው ዓመት ከንግድና ኢንዱስትሪ ፅህፈት ቤት ጋር በጋራ የተወሰዱ ዕርምጃዎች አሉ። በክፍለከተማው በተለይም ሳሪስና ገላን ኮንዶሚንየም አካባቢ ይህ ችግር ጎልቶ ይታያል። አስቀድሞ ከተወሰደው ዕርምጃ በላይ ሥራ የሚፈልግ በመሆኑ አሁንም እንደዚያው ባለ ሂደት ለመሥራት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።
«ብዙ ሥራ ተሠርቷል ግን ወጣቱን ከመጤ ባህል ወረራ አድናችሁታል ወይ? የሚል ጥያቄ ቢነሳ ገና ብዙ መሥራት አለብን ብለን ነው የገመገምነው» ሲሉም አቶ ዳዊት ይናገራሉ። ምንም እንኳን የባህልና ቱሪዝም ጽሕፈትቤቶች በየወረዳው ከተዋቀሩ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ ባይሆንም በአዲስነት ስሜት ብዙ ሥራዎችን መሥራት ስለሚቻል በዚህ ጉዳይ ላይ መረባረብ ያስፈልጋል። በዓመት ጥቂት ቀናትን የሚከወኑ ዝግጅቶችና ስብሰባዎች በየዕለቱ እየደረሰ ያለውን ጥፋት ይቀነሳል ብሎ ማመን አይቻልም። እየሰደዱ መልሶ ማሳደድ ከዚህ እንዳይብስ ግን በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ ያስረዳሉ።

ዜና ሐተታ
ሊድያ ተስፋዬ

Published in የሀገር ውስጥ

 

ስንቶቻችን በከተማችን በሚገኙ መደብሮች ስንሸምት ሚዛኑን እንቆጣጠራለን? ምን ያህሎቻችንስ ስለሚዛን ማጭበርና ስለ ኪሎ ቅሸባ የተፈጸመብንን ለመከላከል ለእራሳችን ዘብ እንቆማለን?  ሁሉም ጥያቄዎች በአዕምሯችን ውስጥ የተለያየ መልስ ሊፈጥሩ ይችላሉ። አብዛኛው ህብረተሰብም ስጋም ሆነ የተለያየ ምግቦች ሲገዛ የሚዛን ጉድለት እንደሚደርስበት ቢያስብ ምን ያህል ኪሳራ ያስከትልብኛል የሚለውን ግን አጢኖ አይገዛም።

 በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የሥጋ ዋጋ 160  እስከ 300 ብር ነው ብለን ብንወስደው፤  ከአንድ ኪሎ ሥጋ ላይ አንድ መቶ ግራም የሚዛን ማጭበርበር ቢደርስብን በዝቅተኛው ስሌት አስራ ስድስት ብር እንደተወሰደብዎት ይቆጠራል። ተጨማሪ ሲገዙ ደግሞ ኪሳራውም በዚያው ልክ እያየለ ይሄዳል። ለአብነት ሥጋ ቤቶቹም በቀን ከአንድ በሬ ላይ ማለትም በግምት ሦስት መቶ ኪሎ ከሚመዝን ሥጋ ላይ በተመሳሳይ መጠን ቅሸባ ቢያደርጉ 30 ኪሎ ግራም ትርፍ ያጋብሳሉ። ይህም በገንዘብ ሲሰላ ህብረተሰቡ በቀን 4 ሺ 8 መቶ ብር  ሊውስዱበት  እንደሚችል ልብ ይሏል። ጉድለቱም ለሸማቹ «እበላ ብዬ ተበላሁ» እንደተባለው ይሆናል። ይህ አሃዝ በከፍተኛው ዋጋ  ካየነው ደግሞ በእጥፍ ሊጨምር እንደሚችል  መገመት ይቻላል።

የኢፌዴሪ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን በአዲስ አበባ የተከናወነውን በሚዛን ላይ ያተኮረ የልኬት ዳሰሳ ጥናት ሰሞኑን ሲያቀርብ በሸቀጣሸቀጥ ሱቆች የተጋነነ የሚዛን ቅሸባ ባይታይም የሥጋ ቤቶች ሚዛን ግን ጉድለቱ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን ይፋ አድርጓል።

የዳሰሳ ጥናቱ 75 ከግል እና ከሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት ችርቻሮ መሸጫ ሱቆች፣ 21 የግል ሥጋ ቤቶች እንዲሁም 12 የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት ሥጋ ቤቶች ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ በጥናቱ መሰረት  የችርቻሮ መሸጫ ሱቆች የከፋ ችግር ባይታይባቸውም አነስተኛም ቢሆን የሚዛን መጓደል እንዳለባቸው ተጠቁሟል። ሊስተካከል ይገባዋልም ተብሏል። የሚዛን የክብደት ልኬት ሁኔታ ጋር በተያያዘ ምልከታ ከተደረገባቸው 33 የግልና የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት ሥጋ ቤቶች ውስጥ 21ዱ ሥጋ ቤቶች ላይ በተለያየ መጠን የሥጋ ክብደት የልኬት ችግሮች ታይቷል። በሥጋ ቤቶቹም በአንድ ኪሎግራም እስከ 143 ግራም ጉድለት የሚያስከትሉ ሚዛኖች ጥቅም ላይ እየዋሉ እንዳሉም ተመላክቷል።

በከተማዋ የሚገኙ ህገወጥ ሥጋ ቤቶች ቁጥር ከግምት ውስጥ ሲገባ  እና በቀን የሚሸጡት የሥጋ መጠን ከፍ ባለ ቁጥር ሸማቹ ህብረተሰብ ለከፍተኛ ብዝበዛ መጋለጥ የሚችልበት ዕድል ሰፊ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ ጥናቱን ያቀረቡት በባለሥልጣኑ የጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ መንግሥቱ ሞላ ናቸው። እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ በጥናቱ ምልከታ ከተደረገባቸው ሥጋ ቤቶች መካከል የልኬት መሳሪያ ብቃት ማረጋገጫ በትክክል የተለጠፈባቸው 12ብቻ ናቸው። አብዛኛዎቹ የመስፈሪያ መሳሪያቸው ብቃት አጠራጣሪ መሆኑ ለማጭበርበር  የተጋለጡ ናቸው። ሚዛኖቹም «አናሎግ» አሠራር ስለሚጠቀሙ በቀላሉ የመዛነፍ ችግር ሊፈጠርባቸው ይችላል። እንደ መፍትሔ በቀጣይ ጊዜያት ብቃታቸው የተረጋገጠ ላቸው «ዲጂታል» ሚዛኖችን መጠቀም በመተማመን ላይ ለተመሰረተ ግብይት ይረዳልና ይህንን ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የገቢ ንግድ ክትትል ባለሙያው አቶ ደመቀ ሰይፉ በበኩላቸው እንደሚያስረዱት፤ ከኑሮ ውድነቱ ጋር የሚዛን ማጭበርበር መኖሩ ህብረተሰቡ ምን ያህል እየተጎዳ መሆኑን ጥናቱ ያሳያል። በተለይ በአብዛኛው ሥጋ ቤቶች በኩል በጥቅም ላይ የሚውሉ «የአናሎግ» የልኬት መሳሪያዎች ለሸማቹ ፊት ለፊት እንዳይታዩ በጎን በኩል ይቀመጣሉ። የልኬት መጠን ጠቋሚዎቻቸው ትክክለኛ በሆነው የዜሮ ምልክት ላይ መነሳታቸውን ወይም ከሚፈለገው የክብደት መጠን ላይ ማረፋቸውን ሸማቹ በትክክል እንዳይመለከት የአቀማመጣቸው ሁኔታ አዳጋች ይሆናል።

ቢሮውም «ዲጂታል» ሚዛኖች ለንግዱ አስፈላጊ መሳሪያዎች መሆናቸውን በማመን ከአስመጪዎች ጋር ለመስማማት ሂደት ላይ እንደነበረ አቶ ደመቀ ያስረዳሉ። ነገር ግን በጨረታ ሂደት ከአስመጪዎቹ ጋር በነበረው ያልተሳካ ግንኙነት ምክንያት ሚዛኖቹን ጥቅም ላይ ማዋል አልተቻለም። በመሆኑም ችግሩን ለመከላከል ተከታታይነት ያለው ቁጥጥርና ፍተሻ ማድረግ ያስፈልጋል። ህብረተሰቡም ስለጉዳዩ ያለውን ግንዛቤ በማስፋት የሚዛን ቅሸባዎችን እንዲከታተል ሰፊ ውይይቶችን ማዘጋጀት እንደገባ ይገልጻሉ።

በአዲስ አበባ በሥጋ ንግድ ላይ የተሰማሩት አቶ ኤልያስ በድሉ ግን ጥናቱ የሁሉንም ነጋዴዎች ሁኔታ ያማከላ ላይሆን ይችላል የሚል ሃሳብ አላቸው። «አንዳንዶች ሚዛኑን አጋድለውና አዛንፈው በማስቀመጥ ሊሸውዱ ይችላሉ። አብዛኛዎቹ ግን ደንበኛ ለመሳብ ሲባል እንኳን እላፊ መርቀው የሚሸጡ ናቸው። በመሆኑም ሸማቹ ህብረተሰብ አታላዮቹን ለመከላከል ሥጋ ከገዛ በኋላ በሌላ ሚዛን በማስመዘን ከአጭበርባሪዎቹ ጋር ያለውን ደንበኝነት ማቋረጥ ይኖርበታል። ከትክክለኛ መዛኞች ጋር ደንበኝነቱን ሲያጠናክርም ሚዛን የሚቀሽቡትን ወደ ትክክለኛው አሠራር ማምጣት ይቻላል» በማለት ህብረተሰቡ ችግሩን ለመካላከል መፍትሔው በእጁ እንደሆነ ያስረዳሉ።

«በጉዳዩ ላይ የስነልክ ጉድለቶችን ተመልክቶ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል አዋጅ እየተዘጋጀ ይገኛል» የሚሉት ደግሞ ከንግድ ሚኒስቴር ህግ ክፍል የመጡት ወይዘሮ ኤልሳ ስዩም ናቸው። በአሁኑ ወቅት ህጉ ተዘጋጅቶ ለተጨማሪ ውይይት እና ውሳኔ ወደ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲላክ ዝግጁ ሆኗል። የስነልክ አዋጁ በንግዱ ላይ የሚስተዋሉ የሚዛን ጉድለቶችንና ተያያዥ ችግሮችን በተመለከተ እርምጃ ለመውሰድ የህግ ድጋፍ ይፈጥራል።

ህብረተሰቡም የሚዛን ችግሩን ቢረዳም ምን ማድረግ እንዳለበት እንደማያውቅ የህግ ባለሙያዋ ይናገራሉ። እንደ እርሳቸው ሃሳብ ከሆነ፤ ህጉ ጸደቆ ቢወጣም የንግድ ግብይቱ ላይ የሚዛን ጉድለቶችን ለመከላከል በዋናነት የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ያስፈልጋል። መገናኛ ብዙሃን እና የተለያዩ የመንግሥት አካላት በጉዳዩ ላይ መድረኮችን ፈጥረው ሸማቹን ሊያስተምሩ ይገባል።

ዜና ሐተታ

ጌትነት ተስፋማርያም

 

Published in የሀገር ውስጥ

በኢትዮጵያ የውጭ አገር ጉዲፈቻን የሚከለክል አዋጅ ወጥቷል። ከአዋጁ መውጣት በጎ ጎን እንዳለው የሚገልጹ እንዳሉ ሁሉ ችግር ፈጥሮብናል የሚሉ አካላትም አልጠፉም። አዋጁ  ካለው ፋይዳ ባሻገር በማሳደጊያ ውስጥ የሚኖሩ ሕፃናትን ዕጣ ፈንታ በተመለከተ  ምን መሠራት አለበት? በሚለው ሃሳብ ላይ የዘርፉ ተዋንያን ሃሳባቸውን ይገልጻሉ።

በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የሚገኙ የሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ኃላፊዎች ሰሞኑን በጉዲፈቻ ላይ አተኩሮ በተካሄደ ውይይት ላይ እንደገለጹት፤ በጉዲፈቻ ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚሠሩ አንዳንድ ኤጀንሲዎች በአዲሱ አዋጅ ላይ ቅሬታ እያነሱ ናቸው። ኤጀንሲዎቹ በእጃቸው ላይ ያሉትን ሕፃናት ቦታ ሳያስይዙ አዋጁ በመውጣቱ የልጆቹ ህይወት አደጋ ላይ መውደቁን ይናገራሉ። የያዟቸውን ልጆችም መንግሥት እንዲረከባቸው በመጠየቅ ላይ ናቸው።

የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር የህግ ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተግይበሉ እንደሚገልጹት፤ የአዋጁ ዋና ዓላማ የሕፃናትን ደህንነት ማስጠበቅ ነው። ሕፃናትም በአገራቸው ብቻ እንዲያድጉ  እና ማንነታቸውንም እንዲያውቁ ሰፊ ዕድል ይሰጣል። በቀደሙ ጊዜያት በጉዲፈቻ በርካታ ሕፃናት ወደ ውጭ አገራት በመላካቸው ከአገራቸው ባህልና ከማህበረሰባቸው ጋር የነበራቸው ግንኙነት ቀንሷል።

በጉዲፈቻ የሚላኩበት መንገድ ህገወጥ ስለነበር ሕፃናቱን በገንዘብ የመለወጥ ተግባር ይፈጸም ነበር።  በተቋሙ የሚደርሱ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት  ከ30 እስከ 35 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ከፈለው የውጭ አገር ሰዎች በጉዲፈቻ ሕፃናትን እንዲወስዱ ያደርጋሉ። መንግሥት ግን አገልግሎቱን ለማግኘት በምዝገባ ወቅት የሚከፈለው ከ25 ብር በላይ አይደለም። በመሆኑም የኤጀንሲዎቹ ጥያቄ መሰረቱ ጥቅምን ፍለጋ ነው ይሉታል።

እንደ አቶ ደረጀ ማብራሪያ፤ አዋጁ ብዙ ሲሠራበትና መፍትሔ ሲበጅለት የቆየ ጉዳይ በመሆኑ  ድንገተኛ ዱብዳ አይደለም። ማንም በውጭ አገር ያለ ዜጋ በአገር ውስጥ ሕፃናቱን ለመደገፍ ከፈለገ የሚከለከልበት አግባብ አይኖርም። ኤጀንሲዎቹ አዋጁ እንደሚጎዳቸው እና ሕፃናቱን እንደሚበተኑ ቢያሳስቡም  በአገር ውስጥ የሚደግፉበትን ሁኔታ አመቻችቶ መሥራት ይቻላል። ምንም የገቢ ምንጭ የሌላቸው ኤጀንሲዎችን ግን ሥራችሁን ቀጥሉ ማለት ከባድ ነውና በተቻለ መጠን ሌሎች አሳዳጊ ድርጅቶችን በማነጋገር መፍትሔ ማበጀት ያስፈልጋል። በጉዳዩ ላይ በአገር አቀፍ  ደረጃ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ በመሆናቸው መፍትሄ ለማበጀት እንደሚቻል ይናገራሉ።

በትምህርት ሚኒስቴር የሴቶችና ሕፃናት ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያና የሕፃናት ደህንነት ቦርድ አባል አቶ ብርሃኑ አረጋ በበኩላቸው፤ የኤጀንሲዎቹ ቅሬታው በሁለት መልኩ ሊታይ እንደሚችል ይጠቁማሉ። ሕፃናትን መሸጥ እንፈልጋለን የሚለው ከሆነ ተገቢነት የሌለው ጥያቄ ነው። ነገር ግን  ለመኖር መሥራት ያስፈልገናል ሌላ አማራጭ ይሰጠን፤ የምንሠራበት ምቹ ሁኔታ ይፈጠርልን ከሆነ ተገቢ ይሆናል። ምክንያቱም በአገሪቱ በሕፃናት ላይ በርካታ ሊሠሩ የሚገባቸው ጉዳዮች ስላሉ ለመኖር መሥራት አለባቸውና ይህንን ጥያቄ ቢያነሱ እንደማይገርም ይናገራሉ።

እንደ ክልሎቹ የሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ኃላፊዎች አስተያየት ከሆነ፤ ከአዋጁ በኋላ በሕፃናት ማሳደጊያዎች በያዙት አቋም ምክንያት በሕፃናቱ ላይ ችግር እንዳይፈጠር ጉዳዩ በትኩረት መታየት አለበት። ምክንያቱም በተቋማቱ ውስጥ ቀድሞ ለጉዲፈቻነት የታሰቡ ህመምተኛ ሕፃናት፣ ልዩ ፍላጎት የሚያስፈልጋቸውና ወላጆቻቸው የማይታወቁ ሕፃናት ይገኛሉ። በመሆኑም  የአገሪቷ ህግ በሚፈቅደው መንገድ ሕፃናቱ አደጋ ላይ እንዳይወድቁ ድጋፍ ማድረግ ይገባል።

አቶ ደረጀ ደግሞ፤ የሕፃናት ማሳደጊያ ተቋማት የተቋቋሙበት ዓላማ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ያሉ ምቹ ሁኔታዎችን ተጠቅሞ የሕፃናቱን ደህንነት መጠበቅ ነው። ይሁን እንጂ 64  በውጭ ጉዲፈቻ ዙሪያ የሚሠሩ አካላት አሁን ላይ መሥራታቸውን በማቆም ላይ ይገኛሉ። ይህ ደግሞ የሚያመላክተው በገንዘብ የራሳቸውን አቅም ለማጎልበት እንጂ የሕፃናት ደህንነት አሳስቧቸው እንዳልነበር በጥናት ባይረጋገጥም መገመት ይቻላል። ስለሆነም በቀጣይም ቢሆን ይህን ሥራቸውን ገንዘብ ለማጋበስ ሊጠቀሙበት ይችላሉና በጥንቃቄ ክትትል ይደረጋል፤ ተግባሩን ሲከውኑ ቢገኙ ህገወጥ የሕፃናት ዝውውር አድርገዋል በሚል ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባም ይናገራሉ።

አቶ ብርሃኑ በበኩላቸው፤ በቀጣይ የሕፃናት ደህንነትን ለመታደግ መጀመሪያ በቤተሰብ፣ ካልተቻለ ደግሞ በማህበረሰቡ ውስጥ እንዲያድጉ ማድረግ ይገባል። አማራጭ ከታጣም በተቋም በማህበረሰቡ እገዛ በአገራቸው እንዲያድጉ ሊደረግ እንደሚገባ ይመክራሉ። ማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍና እንክብካቤን ማስፋፋት፣ የተለያዩ ፕሮግራሞች እንዲከፈቱ ማበረታታት፣ በተለይ አካል ጉዳተኞች ላይ የሚሠሩ ሥራዎችን በባለሙያ በማየትና ጥናት በማድረግ ማስፋት እንደሚያስፈልግ ያሳስባሉ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰሞኑን ባካሄደው ስብሰባ የሴቶችና ሕፃናት ሚኒስትር  ወይዘሮ ደሚቱ ሀምቢሳ ወደ ውጭ በጉዲፈቻ የሚሰጡ ሕፃናት በተገቢው ህጋዊ አሠራር እየተፈፀመ አለመሆኑን ለምክርቤቱ መግለጻቸው ይታወሳል። በጉዲፈቻ የተወሰዱ ሰባት ሺ ሕፃናት ስላሉበት ሁኔታ እና የሚገኙበት አገር መረጃ አልተገኘም። ከአስር ዓመታት በፊት ደላሎች ወላጆችን በማታለልና ከሌሎች አካላት ጋር በመመሳጠር በህገወጥ መንገድ ሕፃናትን ወደ ተለያዩ ሀገራት ልከዋል። በደላሎች ተታለው ልጆቻቸውን ልከው ያሉበትን ያላወቁ ወላጆች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ልጆቻቸውን እንዲያገናኛቸው እየተማፀኑ ናቸው። ሕፃናቱ ለአሳዳጊዎቹ ሲሰጡ በቂ መረጃ እና አድራሻ ያልተያዘ በመሆኑ ፍለጋው አዳጋች መሆኑንም ተናግረዋል።

አቶ ብርሃኑ  በመፍትሔነት ያነሱት፤ ጉዳዩ በየጊዜው የተለየ መልክ ይዞ ብቅ ሊል ስለሚችል ባለድርሻ አካላት ተናበው መሥራት እንደሚኖ ርባቸው ነው። ኤጀንሲዎቹንም እያንዳንዳቸው ዓላማቸውን ሲቀይሩ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግም ያስፈልጋል። ሕፃናት በምንም አግባብ በተቋም እንዲያድጉ አይበረታታምና የማንነት ጥያቄ በሕፃናቱ ዘንድ እንዳይፈጠር፤ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖም እንዳይደርስባቸው ከማህበረሰቡ የጀመረ ሥራ ማከናወን እንደሚያስ ፈልግ ይገልጻሉ።

በጉዳዩ ዙሪያ የሚሠሩ አካላት ቅድሚያ ለሕፃናት ደህንነት የመስጠት ዓላማ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ማሳመን እንደሚገባ የሚገልጹት አቶ ብርሃኑ፤ በበጎ አድራጎትና የሕፃናት እንክብካቤዎች ላይ ተሳትፈው መሥራት እንዲችሉ የሃሳብ ማስለወጥ ተግባር ማከናወን ይገባል። በመሆኑም ተቋሙም ሆነ ሌሎች የማህበረሰቡ ክፍሎች እንዲሁም በጉዳዩ ዙሪያ የሚሳተፉ አካላት ጉዳዩን በቸልታ እንዳያዩት ያሳስባሉ።

 የክልል የሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ኃላፊዎች በመፍትሔነት ያስቀመጡት ሃሳብ፤ በኤጀንሲዎቹ ካሉት ጤናማዎቹ ሕፃናት መካከል በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ውስጥ ገብተው በቀላሉ ሊደገፉ ይገባል የሚል ነው። የልዩ ፍላጎት የሚሹ ሕፃናት ደግሞ ተቋም ተኮር ድጋፍ  እንደሚያስፈልጋቸው ያስረዳሉ። በመሆኑም በአጠቃላይ ሕፃናቱ በማህበረሰብ ውስጥ እና ልዩ ድጋፍ በሚሰጡ ተቋማት ውስጥ ህይወታቸውን እንዲቀጥሉ መታሰብ ይኖርበታል። የኤጀንሲዎቹን ቅሬታም በተለያየ መንገድ መመልከትም ተገቢ እንደሚሆን ይገልጻሉ። መፍትሔው ካልተበጀ ግን የሕፃናቱ ህይወት አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

አቶ ደረጀ በበኩላቸው፤ በፍርድ ቤት ጉዳያቸው ተጀምሮ የነበሩ ሕፃናት ጉዳያቸው ይታይላቸዋል። ነገር ግን ከዚህ በኋላ ምንም ዓይነት የውጭ አገር ጉዲፈቻን የሚመለከቱ አዳዲስ ጉዳዮች አይጀመሩም። በየትኛው ክልል ያሉ ሴቶችና ሕፃናት ቢሮዎች በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ የሚሰጡ እንደማይሆን ያስረዳሉ። አሁን በየኤጀንሲዎቹ የሚገኙ ሕፃናትንም በቀጣይ ወደ ተለያዩ ሕፃናት ማሳደጊያዎች ማሸጋገር ይገባል። ካልሆነ ግን አሁንም ችግሩን በዘላቂነት ለመቆጣጠር አዳጋች ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ።

ዜና ትንታኔ

ጽጌረዳ ጫንያለው

 

Published in የሀገር ውስጥ

ከአስር ዓመት በፊት ነበር በጠዋት አቢ ነፋሻማውን የፔንሴልቬኒያ አየር ለመቀበል ከቤት የወጣችው። በመኖሪያ ቤት ውስጥ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት በአንድነት ተሰብስበው እየተጨዋወቱ ባሉበት ሰዓት ድንገት ነበር የወጣችው። ከዚያ በኋላ በድጋሚ ወደቤት አልተመለሰችም። የአቢ ባልተለመደ ሁኔታ ቀኑን ሙሉ ከቤት መጥፋት ቤተሰቡን አሳስቦታል። ካሁን አሁን ትመጣለች ተብሎ ቢጠበቅም አቢ የውሃ ሽታ ሆና ቀረች።
የቤቱ ሰው ተደናግጦ ፍለጋ ጀመረ። ጎረቤትና ፖሊስ በአቢ መጥፋት ከቤተሰቡ እኩል ተደናግጠው ፍለጋውን አጧጧፉት። አቢ የገባችበት ሳይታወቅ ምስጢር ሆና ቀረች። ለቤተሰቡ የደስታ ምንጭ ነበረች እርሷ ከሌለች ሁሉ ነገር አይደምቅም። ተጫዋች እና ደስተኛም ነበረች። ከብዙ ድካም እና ኀዘን በኋላ ቤተሰቡ አቢ ሞታለች ከአሁን በኋላ እሬሳዋን እንኳን አናገኘውም ብሎ ተስፋ ቆረጠ። ዓመታት ነጎዱ አቢ ተፈጥሮ ነውና በትዝታ ብቻ ልትታወስ በእነ ዴብራ ሲልቬርድ ቤተሰብ ልብ ውስጥ ተቀብራ ተረሳች።
ዓመታት እየነጎዱ እንደ ቀልድ አስር ዓመታት ተቆጠሩ። የጥር 27 ቀን የ2017 ዓመት ግን የእነ ዴብራን የተቀበረ ተስፋ በድጋሚ በተአምር የሚያነሳ ዜና ተሰማ። ስልክ አቃጨለ። ዴብራ ነበረች ያነሳችው። አቢ የምትባል ውሻ አለችሽ። ከወዲያኛው ቀጭን ሽቦ ቤተሰቡን ያስፈነጠዘ ዜና ነበር። ቤተሰቡ ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላ የሚወዷትን ውሻቸውን ማግኘታቸው እጅጉን አስገረማቸው። በህይወት መኖሯ አስገራሚ ነበር። አቢ ይሄን ሁሉ ዓመት ከቤቷ 33 ማይል ርቃ በምትገኘው ፒተስብራ በምትባል ከተማ ውስጥ ጆርጅ በሚባል መልካም ሰው እንክብካቤ በድሎት ስትኖር ነበር።
አቢን ከቤተሰቦቿ ጋር ያቀላቀላት በሰውነቷ ላይ ተቀብሮ የነበረውን ማይክሮ ቺፕስ ነበር። ይህች ቺፕስ በውሾች ሰውነት ላይ የምትቀበር ሲሆን፤ የሩዝ ያክል መጠን ያለው ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ነው። ብዙ ጊዜ ውሾች ከቤታቸው ወጥተው ሲጠፉ በዚህ መሳሪያ አማካኝነት ይገኛሉ። በአቢ ላይ የተቀበረው ግን ለአስር ዓመት ውጤታማ ባይሆንም እንደ ድንገት ተንከባካቢዋ ጆርጅ ቺፕሱን ከአቢ ሰውነት ላይ በማግኘቱ ለቤተሰቦቿ አስረክቧል። ዴብራ ስለ ውዷ ውሻቸው ለኤቢሲ የቴሌቪዥን ጣቢያ ስትናገር «አቢ ከሞት የተነሳች ያህል ነው የተሰማን። ሁሉም ቤተሰብ ይወዳታል። እሷም ሁሉንም ነገር አልረሳችውም ስላገኘችን በጣም ደስ ብሏታል» ብላለች።

ዳግም ከበደ

Published in መዝናኛ

ስለራሳቸው ብዙ መናገርን አይፈልጉም፤ የሠሩትን እንኳን ይህንን ብቻዬን ነው ያደረኩት ማለት አይወዱም። በተለይም «ይህ የሆነው ከእነርሱ ጋር በመሥራቴ ነው» የሚል ምላሽ ይቀናቸዋል። ወሬያቸው ሁሉ እኛ እንዳደረግነው፣ እኛ እንደሠራነው፣ እኛ ይህንን ፈጽመናል ነው። የመጨረሻውን የመምህርነት ማዕረግ እንዳገኙ ባውቅም የሰማሁት ግን እኛነትን በመሆኑ ተገርሜያለሁ። በእርግጥ ብዙ የሚያውቅና ብዙ የሚሠራ ሰው ስለ እራሱ ከሚያወራ ይልቅ ተግባሩ ቢናገርለት ይመርጣል። በተግባር የተደገፈው ሥራቸውም ቢመሰክርላቸው ያስደስታቸዋል።

እንግዳዬም ለዚህ ይሆናል ስለ ራሳቸው ብዙ መናገርን የማይፈልጉት። ይሁን እንጂ «ከእርስዎ ብዙ ነገር ሰዎች ይማራሉ፤ አስተማሪነት ከመደበኛው ትምህርት ውጪም አለ። ስለሆነም ልምድዎን ያስተምሩ፣ ያጋሩ» አልኳቸው። «እኔ ምንም የሚያስተምር ህይወት የለኝም። የሚጠቅምና የሚያስተምር ህይወት አለህ ካልሽ ለመናገር ዝግጁ ነኝ» በማለት ፈቃደኝነታቸውን ሰጡኝ። የዛሬው የህይወት እንዲህ ናት አምድ እንግዳዬ ፕሮፌሰር ኤፍሬም እንግዳወርቅ።
ፕሮፌሰር ኤፍሬም ባለፈው ወር የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሦስት ሰዎችን በሥራቸው መዝኖ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ከሰጣቸው መካከል አንዱ ናቸው። ስለዚህም ጭውውታችንን የጀመርነው «እንኳን ደስ አለዎት» በማለት ነበር። በእርግጥ ብዙዎቹ ለእርሳቸው ይህ ማዕረግ መሰጠቱ «ዘግይቷል» የሚል እምነት አላቸው። ምክንያቱም በርካታ ሥራዎችን አከናውነዋል። ከአገር አልፈው በዓለም ላይ በሚሠሩ ተግባራት ተሳታፊ ናቸው። እውቅናውን ተከትሎ እንዳሉት «ይህ ማዕረግ ለእኔ ሁለት ነገሮችን ይዞ ብቅ ያለ ነው። የመጀመሪያው የበለጠ እንድሠራ የሚያበረታታኝ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ኃላፊነት እየተጫነብኝ መሆኑን አሳይቶኛል። በተለይም ለአገሬ ከዚህ በላይ መሥራት እንዳለብኝ ትዕዛዝ የተላለፈልኝ መሆኑን ነው የምገነዘበው» ሲሉ አጫውተውኛል።
«በዩኒቨርሲቲ ህይወት ውስጥ አንድ ሰው መምህር ሆኖ ሲሠራ አገኘዋለሁ ብሎ የሚያስበው የመጨረሻው ነገር ስለሆነ በጣም ተደስቼበታለሁ። ከእራሴ ይልቅ የተደሰትኩት በተማሪዎቼ ደስታ ነው» የሚሉት ፕሮፌሰር ኤፍሬም፤ መምህርነት ከምንም ነገር በላይ የሚወዱት ሙያ እንደሆነ፤ በተማሪዎቹና በእርሳቸው መካከል ያለው የእውቀት ልዩነት ጠቦ ማየታቸው፤ እንዲሁም አዲስ ነገር ለማግኘትና ሁልጊዜ ለመማር የሚያግዛቸው በመሆኑ እንደሚመርጡት ይናገራሉ። ለአገርም አንድ ነገር ማበርከት እንደቻሉ እንዲሰማቸው እንዳደረጋቸው ነው ያጫወቱኝ። አገሪቱ ብዙ የተማረ ኃይል ያስፈልጋታል። ስለሆነም ያንን ኃይል በአግባቡ ቀርጾ በማውጣት ለአገር ማበርከት ሲቻል ደስተኛ ከመሆን ሌላ አማራጭ የለም ይላሉ።
«ዛሬ ላይ ሆኜ ድሮ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኜ ያስተማሩኝን መምህራን ሳስባቸው እጅግ ደስታ ይሰማኛል። የእነዚህ ሰዎች ጥረት እኔን እዚህ አድርሶኛል። በመሆኑም እኔንም እንዲህ የሚያስቡኝ ልጆችን እያፈራሁ በመሆኔ ሁልጊዜም እደሰታለሁ» ሲሉ ይናገራሉ።
ህልም
ተወልደው ያደጉት ሐረር ከተማ 1957ዓ.ም ሲሆን፤ በወቅቱ የተማረና መምህር የሆነ ወይም በሌላ የመንግሥት ሥራ ላይ ተሰማርቶ የሚሠራ ትልቅ ቦታ ደርሷል ተብሎ ይታመናል። ይህንን ግብ መምታት ብቻ ነበር ህልማቸው። ይሁንና ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በኋላ ነገሩ ተቀየረ፤ ሌላ መሆንንም ተመኙ፤ሌላ ማድረግም ታሰባቸው። ትልቅ የሚባለውን ደረጃ ለመያዝም ይጣጣሩ ጀመር። በተለይም በወቅቱ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ዘርፍ ምንድነው? የሚለው ነገር አሳስቧቸው ነበር። እናም የዩኒቨርሲቲ መምህር መሆኑን ተገንዝበው ገቡበት፤ አደረጉትም።
ፕሮፌሰር ኤፍሬም በእያንዳንዱ ሥራቸው ውስጥ «ይህንን እሆናለሁ» ብለው ሠርተው አያውቁም። ያሰቡት ነገር ላይ ለመድረስ ግን ወደኋላ አይሉም። ሥራው በራሱ ደግሞ መሻሻሎችን ይዞላቸው ብቅ ስለሚል ለያዙት ተግባር የበለጠ ይታትራሉ። ይህ ደግሞ የመጨረሻውን የመምህርነት ማዕረግ አቀዳጅቷቸዋል። ከዚህ በኋላም ቢሆን የበለጠ ለመሥራት ጉልበት እንደሆናቸው ይናገራሉ።
ከቄስ ትምህርት...
ፕሮፌሰር ኤፍሬም እንደዛሬው የአፀደ ሕፃናት ትምህርት ቤት በሌለበት ወቅት ፊደል ለመቁጠር ልዩ ስሙ አደሬ ቲኮ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ቄስ ትምህርት ለመማር ሄደዋል። በዚህም እስከ ዳዊት ድረስ ዘልቀዋል፤ ከዚያም ዘመናዊ ትምህርት ለመማር ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመመዝገብ ሄዱ። ይሁን እንጂ ብዙ ተማሪ በአካባቢው ስላለ ፈተና መውሰድ ግድ ሆነ። የቀረበላቸውን የመግቢያ ፈተና ወሰዱ። ፈተናው ንባብ በመሆኑ ብዙ ተማሪዎች ማለፍ ስለቻሉ ዕድሉ ወደ ዕጣ ተቀየረ።
ይህ በመሆኑ ዕድል ሳይቀናቸው ቀረ። ወደ ቤት ከሄዱ በኋላ ግን ለብዙ ቀናት መቆየት አልቻሉም፤ ቤተሰቡን ካላስገባችሁኝ ሲሉ አስቸገሩ። እነርሱም እፎይታን የሚያገኙት ትምህርት ቤት ሲያስገቧቸው መሆኑን ተገነዘቡና ከቤታቸው በቅርብ ርቀት በሚገኘው ልዑል ራስ መኮንን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲገቡ አደረጓቸው። እዚህም ቢሆን እንደዚያው ፈተናና ዕጣ ነበር። ሆኖም ተሳካላቸውና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታተሉ። ሐረር መድሐኒዓለም አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመግባት እስከ 12ኛ ክፍል ተማሩ።
እዚህ ደረጃ እስኪደርሱ ድረስ በትምህርታቸው ታታሪ ከሚባሉት መካከል አንዱ ናቸው። ሁልጊዜም ከሽልማት ርቀው አያውቁም። ከትምህርት ቤቱ አልፎ ከቤተሰቦቻቸው ሽልማት ይበረከትላቸዋል። ዩኒቨርሲቲ ከገቡም በኋላም ቢሆን ይኸው ሁኔታ ነው የቀጠለው። በዚህ ሥራቸው ዛሬ ላይ የመጨረሻውን የመምህርነት ማዕረግ ማለትም በመድሀኒትና የአካል መስተጋብር የትምህርት መስክ የፕሮፌሰርነትን ማዕረግ አግኝተዋል።
የዩኒቨርሲቲ ቆይታ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ፋርማሲ ትምህርት ቤት የፋርማሲ ተማሪ ሲሆኑ ነበር ከቤተሰብ መለየት የጀመሩት። በዚሁ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሲቀጥሉ ስዊዲን ከሚገኘው ካሮሊንስካ ኢንስቲትዩት ጋራ በጥምረት ስለሚሠራ ስዊዲን በመሄድ ጭምር ትምህርቱን ተከታትለው ውጤታማ ሆነዋል። የፋርማሲ ትምህርት ክፍል የተለያዩ ክፍሎች አሉት። ስለሆነም አንዱን በመምረጥ ስፔሻላይዝድ ማድረግ ስለሚጠበቅባቸው «ፋርማኮሎጂ»ን መርጠው መከታተል ሲጀምሩም በፍላጎታቸው ላይ የተመሰረተ ስለነበር ግባቸው ተሳክቷል። የትምህርት ዓይነቱ የአንድን አካል ውጤታማ ጤንነት ለመጠበቅ መድሐኒቶችንና አካልን መስተጋብራዊ ግንኙነት በሚገባ ማወቅ ነው። ስለዚህም ህመሙን አጥፍቶ በደህናው ጊዜ የነበረን ሰውነት ማምጣት መቻል ስለነበር በሚገባ ተወጥተውታል።
የመድሐኒትና የአካል መስተጋበር ሳይንስን የሚያጠና የትምህርት መስክን ወይም ስነ መድሐኒትና የአካል መስተጋብር ሊባል የሚችለውን ትምህርት በሚገባ በማጥናት ዓለም አቀፍ የምርምር መጽሄቶች ላይ አሳትመዋል። መስኩን የመረጡበት ዋነኛ ምክንያት መድሐኒት ሲሰጥ ወስዶ መጠቀም ብቻ ሳይሆን መድሐኒቶቹ እንዴት አድርገው ይፈውሳሉ? የሚለውን ለማወቅ ስለሚፈልጉ ነው። በመጨረሻ ዓመት ላይ የሚሠራውን የመመረቂያ ጽሑፋቸውንም በዚህ ዙሪያ ያደረጉት ግባቸው መሳካቱን ለማረጋገጥ እንደሆነ አጫውተውኛል።
«መድሐኒት ማግኘት በጣም ደስ ይላል። ሰዎች ድነው ማየት ከምንም በላይ ይማርካል። ድሮ እንኳን ልጆች ሆነን የአገር ባህል መድሐኒት አዋቂ ተብሎ የሚጠራው ሰው ፊታችንን ሲያባብሰንና ስንድን የሚሰማን ስሜት ቀላል አይደለም። እናም እኔም ህመምተኞች ይህ ስሜት እንዲሰማቸው ለማድረግ ስል ይህንን ሙያ መርጫለሁ» የሚሉት ፕሮፌሰር ኤፍሬም፤ አገሪቱ በተፈጥሮ የታደለች ስለሆነች ብዙዎችን የምንፈውስበት መድሐኒት በቀላሉ ማግኘት የምንችልበት አማራጭ እንዳለ ይናገራሉ።
የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ኦስትሪያ ከሚገኘው ከቬይና ዩኒቨርሲቲ እና የድህረ-ዶክትሬት ዲግሪያቸውን እዚያው ኦስትሪያ በሚገኘው ቬይና ሜዲካል ዩኒቨርሲቲ ያገኙት ፕሮፌሰር ኤፍሬም፤ ዶክትሬታቸውን ሲማሩ በፋርማኮሎጂ የሠሩት የመመረቂያ ጽሑፍ ይበልጥ እንዲነቁ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ። ከዚያም የትምህርት መስኩ ይበተናልና አንድ ነገር እንዲመርጡ ተገደው ስለነበር «ኒሮ ሳይንስ» የሚባለውን በመምረጥ ትምህርቱን መከታተል ጀመሩ። ትምህርቱ በአዕምሮ ዙሪያ የሚያጠና ሲሆን፤ አጠቃላይ አካላችንን በመምራት የሚያስተዳድረው እርሱ ስለሆነ በዚህ ላይ እየተማሩና እየተመራመሩ ቆዩ። በተለይም ከዘር ጋር የተያያዘ በሽታ፣ የመርሳትና ከዕድሜ ጋር ተያይዞ የሚመጡ በሽታዎች ላይ በስፋት አተኩረው ይሠሩ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ለሌሎች የተሻገረ እውቀት
መድሐኒት የሚገኘው በሁለት ዓይነት መልኩ ነው። የመጀመሪያው በአጋጣሚ የሚገኝ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በሽታውን ማዕከል ያደረገ ሥራ ማከናወን ላይ የተመሰረተ እንደሆነ የሚያስረዱት ፕሮፌሰር ኤፍሬም፤ አሁን እየተሠራ ያለው በሁለተኛው አማራጭ ነው። በአገር ባህል መድሐኒቶች ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ እየሠሩ መሆናቸውን ይገልጻሉ። በዚህ ዘርፍ በርካታ ምርምሮችን አድርገዋል። በምርምር የታገዙ ሥራዎችንም ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ከ104 በላይ ጽሑፎችን በዓለም አቀፍ መጽሔቶች ላይ አሳትመው እውቀታቸውን አሰራጭተዋል።
በተለይም «ኒሮ ሳይንስ» ላይ ያተኮሩት ሥራዎች የገነኑ ሲሆን፤ በሽታዎች እንዴት ይመጣሉ? መፍትሄያቸው ምን መሆን አለበት? ለመቋቋምስ እንዴት ይቻላል? የሚለውን ይዘት ያካተተ ሥራ በመሥራት ይታወቃሉ። የአገር ባህል መድሐኒቶችን የያዙ፤ በተመሳሳይ ጫት ላይ እየተከናወነ ያለውን ጥናት በሚመለከትም ዓለም አቀፍ መጽሔቶች ላይ አሳትመዋል። የታተሙት ደግሞ በኒሮ ሳይንስ መጽሔቶች ላይ ሲሆን፤ አንዳንዶቹ የአገር ባህል መድሐኒቶች ላይ በሚሠሩ ዓለም አቀፍ መጽሔቶች ላይ ነው።
«የሚፈሰው ጉልበት መጠንና የሚፈጀው ጊዜ የውጤታማነት መሰረት ይሆናል። ምክንያቱም ውጤቱ ትልቅና ትንሽ ይሆናል» ብለው የሚያምኑት ፕሮፌሰር ኤፍሬም፤ ከ20 ዓመታት በላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማስተማር፣ በመመራመር፣ እና ማህበራዊ አገልግሎት በመስጠት ቆይተዋል። ከ100 በላይ የማስትሬት ዲግሪ ተማሪዎችን፣ ሦስት የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪዎችን አማክረውአስመርቀዋል። በአሁኑ ጊዜ ከ20 በላይ የማስትሬት ዲግሪ ተማሪዎችን፤ 10 ደግሞ የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪዎችን በማማከር ላይ ይገኛሉ። በርካታ በአገር ውስጥ እና ውጭ ሀገራት ስብሰባዎች ላይ ተሳትፈዋል፤ ጥናቶችን አቅርበዋል። የበርካታ ማህበራት የቦርድ አባልና የበርካታ ዓለም አቀፍ መጽሔቶች ገምጋሚ ሆነው አገልግለዋል።
ዩኒቨርሲቲውን በተለያዩ ኃላፊነቶች ውስጥ ሆነው መርተዋል፤ አገልግሎትም ሰጠተዋል። ለአብነት በዩኒቨርሲቲው የትምህርት ክፍል ኃላፊ፣ የድህረ ምረቃ ዳይሬክተር፣ የጤናሳይንስ ኮሌጁ ቺፍ አካዳሚ ኦፊሰር ነበሩ። በአሁኑ ጊዜም የፋርማሲ ትምህርት ቤት ዲን ሆነው እየሠሩ ይገኛሉ። በብዙ ዓለም አቀፍ የምርምር ህትመቶች ላይ የአድቫይዘር ቦርድ አባል በመሆንና ሳይንሳዊ ህትመቶች ላይ ይሠራሉ። ከተለያዩ አገራት የሚመጡ የምርምር ሥራዎችን በመገምገምም ይታወቃሉ።
በአገር ውስጥ ደግሞ ፋርማሲ የምርምር ህትመት ላይ የቦርድ አባል በመሆን በተባባሪ ኤዲተርነት ያገለግላሉ። ብዙ ጊዜያቸውን የሚወስደውም ይህ የግምገማ ስርዓቱ ነው። ምክንያቱም አገር አምኖና አዋቂ ነው ብሎ ስለሚልከው እንዲሁም በተለያዩ በጉዳዮች ዙሪያ ጥልቅ ምርምር ያደረገ ሰው ስለሚመለከተው በውሳኔው ጠንቃቃ መሆን፣ በጥልቀት ማየትና አስተያየቱ ጉዳዩን የሚያጎለብት መሆን ይጠበቅበታል። ስለዚህም እርሳቸውም ይህንን ከማሟላት አኳያ ስለሚተጉ ብዙ ጊዜ ይሰጣሉ። ይህንን ሲያደርጉ የአገር ውስጥም ሆነ የዓለም አቀፍ ምርምር ህትመቶች ግምገማ ያደርጋሉ።
ወረቀቶቹ በብዛት የሚመጡት ከአፍሪካና ኤዥያ እንዲሁም ከአውሮፓ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ ከቻይና የሚመጣው እየሰፋ ነው። ተጠናቆ የሚሰጠው በ15 ቀን ውስጥ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮም ሆነ የአፍሪካ ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ በሚያዘጋጃቸው ፕሮግራሞች ላይ ጽሑፎችን ያቀርባሉ። የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቢሮ የሀገረሰብ መድሐኒት ከየት ወዴት የሚለውን መጽሐፍ በሚያዘጋጁበት ወቅት ገምጋሚ ሆነው ሠርተዋል። በኤች.አይ.ቪና መሰል በሽታዎች ዙሪያ በሚዘጋጁ መጣጥፎችና መጽሔቶች ላይ ይሳተፋሉ።
መጀመሪያ ሥራቸውን የጀመሩት ከትውልድ ቀያቸው ብዙም ሳይርቁ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንዳጠናቀቁ አሰበ ተፈሪ ሆስፒታል በፋርማሲስትነት ነው። ከዚያም ሐረር ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ተቀይረው ከቤተሰባቸው ጎን ሆነው ሠርተዋል። ቀጥለውም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ለመማር በአዲስ አበባ ስለመጡ በዚሁ ቀርተው የተማሩበትን ዩኒቨርሲቲ ወደ ማገልገል ገብተዋል።
በልጅነት «ሼፍነት»
በቤት ውስጥ እያሉ እናታቸውን በተለያየ መልኩ ያግዙ የነበሩት ፕሮፌሰር ኤፍሬም፤ እናታቸው ወደ ገበያ ሲሄዱም ሆነ ከቤት ሲወጡ ይህንን አድርግና ጠብቀኝ ይባላሉ፤ የምትሄዱበት ቦታ አይታወቅምና ሁሉን ነገር መሞከር አለባችሁ ይሏቸዋል። እናም እንግዳዬም ቤት ውስጥ ምግብ አብስለው ቤተሰቡን ይመግባሉ። በዚህ ደግሞ ጥሩ ሼፍ እንደሆኑ በቤተሰቡ ተመስክሮላቸዋል። በእርግጥ ልክ እንደእናታቸው እጅ የሚያስቆረጥም ወጥና ሌሎች ምግቦችን አያበስሉም፤ ዓይነቱም ቢሆን የሚከብድና የበዛ አልነበረም። ሆኖም በየጊዜው በሚያደርጉት የመሥራት ጉጉት ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን እንዳይራቡ የማድረግ አቅም ነበራቸው። ይህ ደግሞ አብሮ ተከትሏቸው ተጉዟልና ባህር ማዶ ሲሄዱ ምንም ሳይቸገሩ ምግብ አብስለው እንዲመገቡ ረድቷቸዋል። ሌሎች የአያት ልጅ ቅምጥሎችን እንኳን ሳይቀር ሽንኩርት አከታተፍና ምግብ ማብሰል ያስተምሩ ነበር። ዛሬም ቢሆን ባለቤታቸውን ቀድመው እቤት ከተገኙ ምግብ በማብሰል ያግዛሉ። ይህ የሴት ሥራ ነው የሚል አስተሳሰብ በእርሳቸው ዘንድ የለም። ገበያም ቢሆን ሄደው ለምግብም ሆነ ለሌላ አገልግሎት የሚውለውን አስቤዛ የሚሸምቱት እርሳቸው ናቸው።
አብሮነት
በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እያሉ ህብረተሰብ ትምህርት እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ይሰጣቸው ነበር። እናም ይህንን ተከትሎ «አብሮ መኖር በዓለም ዙሪያ»የሚባልም ተካቶ ይሰጣል። ይህ ደግሞ አብሮነትን ለማጠናከር የሚያግዝ ስለነበር ብዙው ተግባር በድራማ መልክ ይከወናል። ገጸባህሪያቱን ወክለው እንዲተውኑ ይደረጋሉ። በዚህም ማንኛውንም ባህሪ ተላብሰው ቢጫወቱ የተዋጣላቸው ነበሩ። በወቅቱም ምርጥ ተዋናይ የመሆን ህልም እንደነበራቸው ያስታውሳሉ። ይሁን እንጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚለወጡት ነገሮች ሳቢያ እየተውትና ሌሎችን ነገሮች እየተኩበት ሄደዋል።
የህብረተሰብ ትምህርት ማህበራዊ ግንኙነታቸው እንዲዳብር ሁነኛ ሚናን ተጫውቷል። ከሰዎች ጋር የመግባባትና ነገሮችን በህብረት የማድረጉ ጉጉት እንዲያድርባቸውም አስችሏቸዋል። አንድ ነገር የማወቅ ጉጉታቸውም እንዲጨምርና ሁሉንም ነገር መሞከር ለበለጠ ውጤታማነት እንደሚያበቃ የተማሩትም በዚህ ዓይነት ተሳትፎ ውስጥ በማለፋቸው ነው። በባህሪ በጣም አስቸጋሪ ከሚባሉት ተርታ እንዳይመደቡ፤ ዝምተኛና ነገሮችን አገናዝቦ መወሰንን እንዲጀምሩ ያደረጋቸው ይህ ተሳትፏቸው ነው።
«ልጅነትን ዳግመኛ ባስባትና ዕድሉን ባገኝ ማየት የምፈልገው ነፃ የሆነ ሃሳብን ማራመድን፣ አለመጨነቅና አለማዳላትን እንዲሁም ንጹህ ልብን ይዞ መጓዝን ነው። ስለ እኔ የሚያስበውም ብዙ ስለሆነ ችግሮችን በቀላሉ ማለፍ እችልበታለሁና ይናፍቀኛል» በማለት የልጅነት ዘመናቸውን የሚያስታውሱት ፕሮፌሰር ኤፍሬም፤ በልጅነት ዕድሜያቸው የእግር፣ የእጅና የቅርጫት ኳስ በመጫወት የሚያክላቸው አልነበረም። በብይ ጨዋታም ቢሆን የተካኑ ነበሩ። ቼዝ መጫወትም በጣም ያስደስታቸዋል። በውድድር ባይደገፍም ጥሩ ተጫዋች መሆናቸውን ለማመላከት ለትምህርት በሄዱባቸው ቦታዎች፣ እንዲሁም ኮንፍረንሶች ላይ ሲሳተፉ ተጫውተው ያሸንፋሉ። እሁድ እሁድ ሥራ ካልበዛባቸው ጓደኞቻቸውን፣ ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን በመያዝ እንጦጦ ላይ መናፈስን ይመርጣሉ።
ፍቅር በአጋጣሚ
ለሥራ ጅጅጋ በተመደቡበት ወቅት ነበር የዛሬዋን ባለቤታቸውን ያገኟት። አብሯቸው የተመረቀ የልብ ጓደኛቸው ጋር ሲመላለሱ ዓይናቸው አረፈባት፤ ልባቸውም ተመኛት። ግን ደግሞ የጓደኛቸው ሚስት እህት ነችና እንዴት ይህንን ማድረግ ይቻላቸው፤ ግራ ተጋቡ። ነገር ግን ወደዋት ነበርና ያሰቡትን ከማድረግ ለመቆጠብ አልቻሉም። እናም ቅድሚያ ለሚወዱት ጓደኛቸው ጉዳዩን አጫወቱት። እርሱም ተስማማና ቅርርቡ ተጠናከረ። ጎልብቶም ለትዳር በቃ። በዚህ ደግሞ ዛሬ ድረስ የማይቆጩበትን ተግባር እንዳከናወኑ ይሰማቸዋል። ምክንያቱም ባለቤታቸው ለስኬት እንዲበቁ ሁልጊዜም ትተጋለች።
ለባሏም ሆነ ለልጆቿ ትልቅ ክብር አላት። ይህ ደግሞ በቤት ውስጥ ምንም ዓይነት መቃረን ሳይፈጠር 21 ዓመታትን እንዲያሳልፉ አድርጓቸዋል። ሦስት ልጆች አፍርተዋል።
«ልጆቼን በራስ የመተማመን ባህላቸውን ነጥቄ ማሳደግ አልፈልግም። ምክንያቱም የቀደምነው ልጆች ያጣነው ብዙ ነገር አለ። እንደፈለገን እንድንናገር አይፈቀድልንም፤ ጎረቤት ወይም ትልቅ ሰው በአካባቢው ካለ ተደብቀን እንድንቀመጥ ወይም ወደውጪ እንድንወጣ ይደረጋል። ይባስ ብሎ መናገር ባለብን ጉዳይ እንኳን ዕድሉ አይሰጠንም። አንተ ልጅ ነህ፣ ልጅ ፊት... እያሉ ያርቁናል» የሚሉት ፕሮፌሰር ኤፍሬም፤ ከቤተሰብ መማር የሚገባቸውን ባለማግኘታቸው ስለሚቆጫቸው ልጆቻቸው በራሳቸው እንዲወስኑ አድርገው እንዳሳደጓቸው ይናገራሉ።
በእርግጥ ይህንን ባህል ሙሉ ለሙሉ መቃወም ተገቢ አይደለም። ምክንያቱም በእያንዳንዱ ነገር ላይ ቁጥብነትን ያስተምራል፤ ለሰዎች አክብሮት እንዲኖረንም ያደርጋል እንዲሁም ቅድሚያ ለራስ የሚለውን ነገር አስቀርቶ አንተ ትብስ የሚለውን ባህሪ እንድንላበስም ዕድል ይሰጣልም ሲሉ አጫውተውኛል። የአንድ ሴት ልጅና የሁለት ወንድ ልጆች አባት የሆኑት ፕሮፌሰር ኤፍሬም፤ ሁለቱ ልጆቻቸው ዩኒቨርሲቲ የገቡ ሲሆን፤ እንደቀደመው ዛሬ ላይ የልጆችን ውሳኔ በቤተሰብ ጫና ማስቀየር አይቻልምና ፍላጎታቸውን ያማከለ ምርጫ እንዲኖራቸው አድርገዋቸው እንደነበር ይናገራሉ።
የመጨረሻው ልጅም ቢሆን የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፤ «የዛሬ ልጅ ከእኛ ጊዜ ልጅ የተለየ ነው። ድሮ ተምሮ ራሱን ማውጣት ከቻለ ብቻ ነው ኑሮን በራሱ የመምራት አቅም ይኖረዋል የሚባለው። ዛሬ ግን ባይማርም የራሱን መስመር ይዞ በተለያየ መልኩ ተሰማርቶ ራሱን ማሸነፍ ይችላልና ሥራውን በትምህርት እንዲያግዝ ማድረግ ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሠራ አደርጋለሁ» ብለውኛልም።
«የቤት አባወራነትን በሁለት መልኩ ማየት ያስፈልጋል። የመጀመሪያው በቤት ውስጥ ጊዜ ሰጥቶ ማሳለፍ ልኬታው ምንድነው? የሚለው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ቤተሰብ በሚገባውና በሚረዳው ልክ ቤቱ ላይ ምሰሶ የሚሆን ተግባር መከወን ነው። ስለዚህም ከዚህ አኳያ ሲታይ በሚፈለገው ልክ ነኝ ባይባልም አይደለሁም ማለት ግን አይቻልም። ቤተሰቦቼ ባማሳልፈው ተግባር እጅግ ደስተኞች ናቸው። ውሎዬንም በሚገባ ይደግፉታል። በተለይ ባለቤቴ ሥራን ለኑሮዬ በሚመች መልኩ ስለማውለው ታግዘኛለች እንጂ አትከፋብኝም፤ ጊዜ አትሰጠኝም የሚል ነገር አታነሳም። ልጆቼም ቢሆኑ እንዲሁ ናቸው» የሚሉት ፕሮፌሰር ኤፍሬም፤ ጊዜ ሲያስፈል ጋቸውም ፈቃድ እንዲጠይቁ ግልጽ የሆነ ጥያቄ ማቅረባቸውን፣ ዘና ማለት ሲፈልጉም አብረዋቸው እንደሚሄዱና ብዙም ባይሆን ደስተኛ እንደሚያደርጓቸው ይናገራሉ። ሥራው በሰዓት የተገደበ ባለመሆኑ ግን የሚፈለገውን ጊዜ ሰጥቻለሁ ብለው እንደማያምኑም ነው ያጫወቱኝ።
ሽልማትና የቀጣይ እቅድ
በኢትዮጵያ ፋርማሲ ማህበር አንድ ጊዜ የዓመቱ ምርጥ ተመራማሪ በሚል ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በተለያዩ የምርምር ሥራዎቻቸውና በተሳተፉባቸው መድረኮች ሁሉ እንዲሁም ባማከሩበት ዘርፍ በርካታ የምስክር ወረቀቶችን አግኝተዋል። ዛሬ ደግሞ የመጨረሻው የመምህርነት ማዕረግ ፕሮፌሰርነትን ከዩኒቨርሲቲው አግኝተዋል። «ሽልማቴ ተማሪዎቼ ናቸው። ሁልጊዜ በአዲስ መርህ ተራምደው ለአገራቸው አዲስ ነገር ሲያበረክቱ ማየት ለእኔ ትልቁ ሽልማቴ ነው» የሚል እምነት አላቸው። ይህንን አስቀጥሎ ለመሄድ ደግሞ የቀጣይ በርካታ እቅዶችን ይዘዋል። በጥምረት የሚሠሩ ሥራዎቹን ማስቀጠል አንዱ ሲሆን፤ በሀገረሰብ መድሐኒቶች ዙሪያ በርካታ የምርምር ሥራዎች ተከናውነዋልና እነዚህን ሥራዎች ወደ ፋብሪካ ሄደው አገልግሎት የሚሰጡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ይናገራሉ።
መልዕክት
የፋርማሲ ሙያ የተለየ ተሰጥኦን የሚጠይቅ ነው። ምክንያቱም በአመለካከት ብቃት የሚወሰን ነው። ስለዚህም ንግድንና ሙያን አቀናጅቶ መጓዝ አስቸጋሪ ነው። መድሐኒት ከመሳሪያ ቀጥሎ ለደህንነት አጋዥ የሆነ መሳሪያ ነው። እናም የሰውን ህይወት ለመታደግ ተብሎ የማይተገበር ከሆነ እንደሌሎች ሸቀጦች እንጂ እንደ መድሐኒት አይሆንም። ትርፍ የሚገኝበት ሰዎችን በማትረፍ እንጂ ገንዘባቸውን እንዲያፈሱና እንዲገኙ በማድረግ መሆን የለበትም።
የፋርማሲ ትምህርት የተለየ ሸቀጥ የሚከናወንበት ነው። ስለሆነም የተለየ ትምህርትና የተለየ ስነ-ምግባር ያስፈልገዋል። ይህንን የተማረም ሰው ልዩ መሆን ይጠበቅበታል። ነገር ግን ባለሙያ ያልሆነ ሰው የመድሐኒት እደላ ያደርጋል፣ ህጋዊ ያልሆኑ መድሐኒቶች በስርጭት ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል። ብዙ በዚህ ዙሪያ የሚሠሩ ትክክል ያልሆኑ ተግባራት አሉ። እናም እነዚህን ለመፍታት በማህበሩ ደረጃ ሦስት ነገሮች ላይ ጥናት ለማድረግ እየታሰበ ነው። እነርሱም የባለሙያው ጥንካሬ ላይ፣ ትምህርት ጥራቱና ስነምግባር ላይ ሲሆኑ፤ ከጥናቱ በኋላ የሚገኘውን ውጤት ማዕከል በማድረግ የመፍትሔ አቅጣጫ የሚቀመጥ ይሆናል። ነገር ግን አሁን ላይ ከመስማት ባለፈ ይህን አድርጉ ማለት ይከብዳል። የእያንዳንዱ ሰው አመለካከት በጉዳዩ ዙሪያ መቀየር እንዳለበት ይታመናል። ለሰዎች እንጂ ለገንዘብ ትኩረት መስጠት ቅድሚያ መሰጠት የለበትም፤ የሚለውን ሁሉም መውሰድ ይኖርበታል። ሃሳብን ወደ ተግባር ለመቀየር እጅግ ፈታኝ የሚሆነው የአቅርቦት ችግር ስለሆነም በአገሪቱ ያለው ተመራማሪ የሃሳብ ችግር ስለሌለበት በዚህ ዙሪያ አገሪቱ መሥራት ይጠበቅባታል ይላሉ።
«ከአፀደ ሕፃናት ጀምሮ መሠራት እንዳለበት አምናለሁ። እዚህ ደረጃ ላይ የሚሠራው ያልተማረና ሥራ የሌለው ነው። ከመሰረቱ ያልተያዘ ነገርን ከቆመ በኋላ ማቃናት እጅግ ከባድ ነው። አሁን ላይ እገሌ እንዲህ ሆነ ቢባል ብዙ አይጠቅምም። ለዚያ ሰው መበላሸትም ሆነ ደህንነት መሰረቱ መነሻው የሚሆነው። አገሪቱ ትኩረት አድርጋ ልትሠራበት የሚገባው በተማረ ኃይልና ጠባቂ ባልሆነው ሰው ታች ላይ የሚማሩትን ልጆች ማቅናት መሆን ይኖርበታል። ዛሬ ላይ እኔና መሰሎቼ ለዚህ የበቃነው በራሳችን ጥረት በመሆኑ ይህ ትውልድ ይህንን ያህል መስዋዕትነት መክፈል የለበትም»ይላሉ። ከእንግዳዬ ጋር ብዙ ቁም ነገሮችን ተጨዋውተናል። ይሁንና ጊዜና ቦታ ገደበኝና ከህይወት ተሞክሯቸው ጥቂቱን አካፈልኳችሁ። መልካም ዕለተሰንበት!

 

ጽጌረዳ ጫንያለው

Published in ማህበራዊ
Sunday, 11 February 2018 00:23

ኪነ ጥበብ ዜና፤

«ፍቅር እስከመቃብር» መጽሐፍ ላይ ውይይት ይካሄዳል
በደራሲ ሃዲስ አለማየሁ «ፍቅር እስከ መቃብር» ልብወለድ መጽሐፍ ላይ ያተኮረ ውይይት የዛሬ ሳምንት ዕሁድ የካቲት 11 ቀን 2010ዓ.ም ከቀኑ በ8፡00 ሰዓት በኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ /ወመዘክር/ አዳራሽ እንዲካሄድ ቀነ ቀጠሮ ተይዞለታል።
ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ የመጻሕፍት ንባብና ውይይት ዝግጅት ክፍል ከኢትዮጲስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር የመጽሐፍ ውይይቱ አዘጋጅተውታል። በውይይቱ ላይ የስነ-ጽሑፍ ባለሙያውና መምህሩ አቶ መሰረት አበጀ «የግፍ መርህ ዳፋ - የሀዲስ አለማየሁ ደወል (በፍቅር እስከመቃብር)» በሚል ርዕስ ጽሁፍ የሚያቀርቡ መሆኑን ከሚዩዚክ ሜይዴይ አቶ ስንታየሁ በቀለ መረጃውን አድርሶናል።
«ድሮና ዘንድሮ» ልዩ ዝግጅት ረቡዕ ይካሄዳል
ለረጅም ዓመታት በፍቅርና በትዳር ህይወት ጸንተው የቆዩ ባለትዳሮች ልምዳቸውን እንዲሁም ለትዳራቸው ስኬት ያበቃ ምሥጢራቸውን የሚያካፍሉበት መርሃግብር ሊዘጋጅ ነው። «ድሮና ዘንድሮ» የተሰኘው መርሃ ግብሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን የፍቅረኛሞች ቀን ምክንያት አድርጎ ይዘጋጃል።
በአብርሃም ግዛው ኢንተርቴይመንት የተዘጋጀው ፕሮግራም በኔክሰስ አዲስ ሆቴል ረቡዕ የካቲት 7 ቀን 2010ዓ.ም ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል። ይህ ዝግጅት የተለያዩ ስነ-ጽሑፋዊ ሥራዎች ይቀርቡበታል። የኮሜድያን ሥራዎች እንዲሁም አንጋፋ የጥበብ ሰዎች ይሳተፉበታል። መግቢያ ዋጋውም 1ሺ300 ብር መሆኑን አቶ አብርሃም ግዛው ነግረውናል።
«ንጉሥ ዘርዓያዕቆብ» እና «የህሊና መንገድ» ለንባብ ቀረቡ
በአንዱአለም አባተ (የአፀደ ልጅ) የተጻፉት «ንጉሥ ዘርዓያዕቆብ» እና «የህሊና ደወል» የተሰኙ ሁለት መጻሕፍት ለንባብ በቅተዋል።
እንደ ቅደም ተከተላቸው የወጎች እና የአጫጭር ልብወለዶች ስብስብ የሆኑት መጻሕፍቱ፤ 124 እንዲሁም 118 ገጾች አላቸው። በመጻሕፍት ገበያም 60 እና 50 ብር ዋጋ ይገኛሉ።
የሪቻርድ ፓንክረስት
ዶክመንተሪ ተመረቀ
የኢትዮጵያን ታሪክ በማጥናት የሚታወቁት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትን በተመለከተ የተዘጋጀው ዶክመንተሪ ተመረቀ፡፡ ከትናንት በስቲያ የካቲት 2 ቀን በጀርመን የባህል ማዕከል በርካታ ታዳሚዎች በተገኙበት ተመርቋል፡፡
ዶክመንተሪው የድምፅ ቀረጻ እና ፎቶዎች የተካተቱበት ሲሆን፤ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትን በቅርበት የሚያውቁ ሰዎች፣ ቤተሰቦቻቸውና የታሪክ ባለሙያዎች አስተያየት ተካቶበታል፡፡ የቀድሞ ወዳጆቻቸው እነፕሮፌ ሰር እንድሪያስ እሸቴም በምርቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል፡፡ ዶክመንተሪውን ያዘጋጀው ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ሲሆን፤ ዶክመንተሪውን ለማዘጋጀት አንድ ዓመት ፈጅቶበታል፡፡
በምረቃ ስነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደ ማርያም ‹‹የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የሕይወት ታሪክ ታሪካችን ነው፤ ሥራዎቻቸው ደግሞ ቅርሳችን ነው›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ከዶክመ ንተሪው አዘጋጅ እዝራ እጅጉ የታሪክ ሰነዶችን የያዙ ሲዲዎች ለሚኒስትሯ ተሰጥቷል፡፡

Published in መዝናኛ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።