Items filtered by date: Monday, 12 February 2018

ከአገሪቱ ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ በ900 ኪሎሜትሮች እንዲሁም ከትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ በ118 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የምትገኘው ዓዲግራት ከተማ ከ 120 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን በጉያዋ አቅፋ የያዘችና ወጣ ገባ በሆነው መልከዓ ምድራዊ አቀማመጧ የምትታወቅ ከተማ ናት፡፡ ዙሪያዋን በአይጋ፣ አሲምባ፣ የምጉላት፣ ኣሎቃ፣ ገረኣልታ ሰንሰለታማ ተራሮች እንዲሁም ከአንድ አለት ተፈልፍለው በተሰሩ ገዳማት የተከበበችው ይህች ከተማ በርካታ ጎብኚዎች እንደሚጎርፉባት ይነገራል፡፡ ታዲያ ከአገር ውጪ ጎብኚዎች በተጨማሪ ለልማት በንቃት ተሳትፎ በሚያደርገው ነዋሪዋ ምክንያት ለተሞክሮ ልውውጥ ከዘጠኙም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የሥራ አመራሮች ከሰሞኑ ከትመውባት ነበር፡፡ እኛም ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኅብረተሰብ ተሳትፎው ለመልካም አስተዳደር መስፈን እያበረከተ ያለውን አዎንታዊ አስተዋፅዖ ለመዳሰስ ወደድን፡፡ በዚህም በአሁኑ ወቅት ያለውን ነባራዊ ሁኔታና በቅርብ እየተደረገ ያለውን ጥልቅ ተሃድሶም በማከል ከከተማዋ ነዋሪዎችና ከተለያዩ አካላት ጋር ያደረግነውን ቆይታ ለንባብ እንዲመች አድርገን እንዲህ ይዘንላችሁ ቀረብን፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች
አቶ ኃይለማርያም ዮውሓንስ በአዲግራት ከተማ ቀበሌ አምስት ነዋሪ ናቸው፡፡ በአካባቢያቸው እየተደረገ ባለው የአካባቢ ልማት ሥራ ላይ ተሰማርተው ነው ያገኘናቸው፡፡ ስለአካባቢው የልማት ሥራ ጠይቀናቸው በሰጡን ምላሽም “ሕዝቡ የሥራ ፍላጎት ያለው በመሆኑ በእያንዳንዱ የልማት ሥራዎች ተሳትፎውን ያደርጋል፡፡ ለዚህም በአሁኑ ወቅት ያለው ሰላም አስተዋፅዖ አድርጓል፡፡ ነገር ግን በአገር ላይ በአሁኑ ወቅት ብልጭ ድርግም ሲሉ የሚስተዋሉት የሰላምና መረጋጋት ችግሮች መንግሥት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ልማትም ሆነ መልካም አስተዳደር ያለ ሰላም መስፈን አይችሉም”፡፡
በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ መንግሥትን ቀድሞት አልፏል የሚሉት ነዋሪው መንግሥት በሚፈጠሩ ችግሮች ላይ አፋጣኝ እርምጃ ያለመውሰድና መለሳለሶችም ይታዩበታል ባይ ናቸው፡፡ በአገሪቱ እየመጡ ያሉ ልማቶችን ብሎም ራሱ የሚጠቀምባቸውንና አገልግሎት የሚያገኝባቸውን መሠረተ ልማቶች እሚያቃጥሉ አጥፊዎች እየተፈጠሩ ነው፡፡ በተግባር የሚሳተፉት ደግሞ ወጣቶች ሲሆኑ ዋነኛው መነሻ አሁን ያለው ትውልድ ስለ ሰላም ያለውን ዋጋ ባለመረዳት በመሆኑ መንግሥት በትምህርት ጭምር እንዲሰጥ ማድረግ እንደሚገባው ይናገራሉ፡፡
በከተማዋ በተለያዩ ተቋማት ያሉ አገልግሎት አሰጣጦችም ላይ የሚታዩ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ሳይናገሩ አላለፉም፡፡ በተለይ ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንፃር በፍጥነት ውሳኔ አለመሰጠቱና ወደ ሥራ እንዲገቡ አለመደረጉ ማነቆ ሆኗል፡፡ በተያያዘ ሥራ ከመጀመራቸው አስቀድሞ ያለው የብድር አቅርቦት ወደ ሥራ ከገቡ በኋላም የሚታዩ ለሥራቸው ተገቢውን ክፍያ በወቅቱ አለመፈፀም ችግሮች ቅሬታዎችን እያስነሳ ይገኛል፡፡
መንግሥት የሚነሱ ችግሮችን ለማረምም በተለያዩ ጊዜያት ራሱን ፈትሿል፡፡ በቅርቡ ባደረገው ጥልቅ ተሃድሶም ለውጦች እንደሚመጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ዕምነት እንዳላቸው ይገልፃሉ፡፡ ነገር ግን ለማቃለል በተለይ ተጠያቂ ማድረግ ላይ ሊሰራ ይገባል፡፡ እንደከዚህ ቀደሙ ችግር ውስጥ ተዘፍቆ ኅብረተሰቡን ሲበድል የነበረ አመራርን ቦታ መቀየር ሳይሆን በጥፋቱ ልክ ተጠያቂ ማድረግ ላይ በአንክሮ ሊመለከት ይገባል ይላሉ፡፡
በቀበሌ ሦስት ልዩ ስሙ አድሽ ዓዲ ነዋሪ ወጣት መብርሃቱ ገብረመድህን በበኩሉ በከተማዋ የሚገኘው በርካታ ወጣት የሥራ ዕድል እንዲፈጠርለት ከፍተኛ ፍላጎት ያለው ቢሆንም በዚህ ረገድ የሚታዩ ክፍተቶች ግን መኖራቸውን ይናገራል፡፡ መንግሥት የሥራ ዕድል ለመፍጠር ባመቻቸው ጥቃቅንና አነስተኛም ለመደራጀት የሚመረጡት ዘርፎች ውስን መሆን ችግር ሆኖባቸዋል፡፡ በስፋት ያለው ዘርፍም ኮብልስቶን መሆኑ ወጣቱ በሚፈልገው ተደራጅቶ ውጤት እንዳያመጣ ያደርገዋል፡፡ በዚህም ወጣቶች ሥራ ፈላጊ ሆነው ቁጭ ይላሉ በማለት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ያብራራል፡፡
ሌሎች ስለ ከተማዋ
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የወጣቶች ፌዴሬሽን ረዳት ጸሐፊ ወጣት አብርሃም መሀሪ የዓዲግራት ከተማ በርካታ አስደናቂ ነገሮች እንዳሏት መመልከቱን ያስረዳል፡፡ ከተማዋ ውስጥ ለውስጥ መንገዶቿ በኮብልስቶን ከመነጠፍ በተጨማሪ አንድም ቆሻሻ ተጥሎ አለመታየቱ ግን የበለጠ ውብ እንድትሆን አድርጓታል ይላል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም የመንገድ ሥራዎች ላይ ኅብረተሰቡ የራሱን አስተዋፅዖ ሲያበረክት መመልከቱ ግርምትን ጭሮበታል፡፡ ኅብረተሰቡ የራሱን ድርሻ በአግባቡ መወጣት እንደቻለም ለመገንዘብ ችሏል፡፡
እንደ ወጣት አብርሃም ገለፃ፤ በከተማዋ ያሉት ሥራዎች አስተዳደሩ ከሕዝቡ ጋር ያለው ቅንጅታዊ የሁለትዮሽ ግንኙነትና አንድነት መኖር ምስካሬ ይሰጣሉ፡፡ መንግሥትና ሕዝብ ተናበው እንደሚሰሩም ያሳያል፡፡ የሚታየው ሥራም ለታይታ ሳይሆን ችግር ለመቅረፍ ከውስጥ በዘለቀ አገራዊ ፍቅር የመነጨ በመሆኑ ለሌሎችም ተሞክሮ ይሆናል፡፡ በተለይም አረጋውያን፣ ሲቪል ሰርቫንቱና የሃይማኖት ተቋማት ጨምሮ በነቂስ ወጥቶ በስፋት የሚያደርገው ርብርብ ልምዱ ሊሰፋ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ልማቱ እንዲፋጠን የበኩላቸውን የሚወጡ የሃይማኖት ተቋማትም በጋራ ተሰባስበዋል፡፡ በአገሪቱም ወጥነት ባለው ሁኔታ ኅብረተሰቡን አነቃንቆ ወደ ልማቱ ማስገባት ከተቻለ ለውጡን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማምጣት ይቻላል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በማንሳት በዚሁ መነሻነት ልማት ሲወድም መመልከት እየተለመደ መምጣቱን እንደታዘበ የሚገልፀው ወጣት አብርሃም አገርን ወደ ኋላ ጎታች ድርጊት የሚፈፅሙ ተግባራትን ለማስቆም የአመራሩ ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው፡፡ በመሆኑም ከከተማዋ ሁለንተናዊ የኅብረተሰብ ተሳትፎ ተሞክሮ ሊወሰድ ይገባል በማለት በክልሉ አንድነት የመፈጠሩ ምክንያት ተቀራርቦ መስራቱ መሆኑን ይጠቁማል፡፡
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ሙሉጌታ ስመኝ እንደሚናገሩት፤ በዓዲግራት ከተማ ኅብረተሰቡ በተለይ በመሠረተ ልማት በፅዳትና ውበት እንዲሁም አረንጓዴ ሥራዎች የነቃ ተሳትፎ አለው፡፡ በዚህ ውስጥም የባለቤትነት ስሜት ስለሚይዝ ልማቱን ማፍረስ ላይ ሳይሆን ተጨማሪ የመልማት ፍላጎቱን ማሳደግ ላይ ትልቅ አስተዋፅዖ ያደርጋል፡፡
በከተማዋ ውስጥ ለውስጥ ዞረው ቢመለከቱም ምንም ዓይነት ቆሻሻ እንዳልተመለከቱ የሚያስረዱት አቶ ሙሉጌታ ተግባሩ የሥልጡን ሕዝብ መገለጫ ነው ይላሉ፡፡ ይህም በኅብረተሰቡ ንቃተ ህሊና ማደግ ላይ የክልሉ መንግሥት የሰራቸው በርካታ መልካም ተግባራት እንዳሉ ያመላክታል፡፡ የሚሰሩ የልማት ሥራዎችን ኅብረተሰቡ ላይ የባለቤትነት ስሜት መፍጠር ካልተቻ ዞሮ ያፈርሰዋል፡፡ ነገር ግን ግንዛቤ ከማሳደግ ጎን ለጎን ተሳታፊ ከተደረገ እንዲንከባከባቸው ይደረጋል፡፡ በመሆኑም በመላው አገሪቱ ተመሳሳይ ለውጥ ለማምጣት በሁሉም ክልሎች መሰል ተግባራት ሊለመዱ ይገባል፡፡ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በየደረጃው እየፈቱ ለመሄድ በከተማው የታየው ተቀራርቦ መስራት ተሞክሮ ሊሰፋ ይገባል በማለት እርሳቸውም ወደ ክልላቸው ተሞክሮውን ለማስፋት ዝግጁ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የፊቼ ከተማ የማዘጋጃ ቤት ኃላፊ አቶ ያሬድ የሺጥላ በዓዲግራት ከተማ የተሻለ ተሞክሮ እንደቀሰሙ ይናገራሉ፡፡ ኅብረተሰቡ ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ ልማቱን የራሱ ተግባር አድርጎ በባለቤትነት ይሰራል፡፡ ገና ከሌሊቱም ደጃፉን ሲያፀዳና ቆሻሻም ከማጠራቀሚያ ውጪ ተጥሎ ለማየት እንዳልቻሉ ይጠቁማሉ፡፡
የመልካም አስተዳደር አንዱ መርህ የሆነው የሕዝብ ተሳትፎ ላይ ክፍተቶች በመኖራቸውም በአሁኑ ወቅት ለሚታዩት የሰላምና አለመረጋጋት ችግሮች ምቹ መደላደል እየፈጠሩ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ኅብረተሰቡ ይህን መሰል ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ሲችል ማህበረሰቡ ራሱ ለራሱና ለአገሩ የሰላም ዘብ መሆን ይጀምራል፡፡ በመሆኑም በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ለሚሰሩ ተግባራት ኅብረተሰቡን ማሳተፍ ወደ ጎን ሊተው ሳይሆን በልዩ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተሞክሮ መውሰዳቸውን ያስረዳሉ፡፡
ከተማዋ በመልካም አስተዳደር
በከተማዋ የሕዝብ ግንኙነት መኮንን አቶ የማነ ተክለማርያም እንደሚያስረዱት፤ በከተማዋ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎችና በክልሉ እንደሚነሳው የመልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ይነሳል፡፡ ኅብረተሰቡ ከሚያነሳው ጥያቄዎችም የተፈቱና በመንገድ ላይ ያሉ እንዲሁም ትልቅ አቅምን የሚጠይቁና ቀጣይ ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን ለመፍታት የዕቅድ አካል ተደርገው የሚሰራባቸው ጥያቄዎች አሉ፡፡
በአገልግሎት አሰጣጥ
ከመልካም አስተዳደር ጥያቄዎቹ መካከል አንዱ በመንግሥትና በግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ያለ የአገልግሎት አሰጣጥ መሆኑን አቶ የማነ ያስረዳሉ፡፡ ከተሀድሶ አስቀድሞ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት አልፎ አልፎ ኅብረተሰቡ በሰዓቱ ለተገልጋይ ቢሮን ክፍት አድርጎ የተገልጋይን ጥያቄ ለማዳመጥ ዝግጁ መሆን ላይና ውሳኔ የመስጠት ብቃት ላይ ጥያቄ ይነሳል፡፡ ይህም የመነጨው ተገልጋይን በማስተናገድ ምትክ ቢሮዎች ዝግ መሆንና ስብሰባ ላይ ናቸው በሚሉ ምላሾች ተገልጋዩ ለእንግልት በመዳረጉ ነው፡፡
ፈፃሚው አካል የተለያዩ ማህበራዊ ሰበቦችን በማብዛት ቢሮ ዝግ ከማድረግ ባለፈ ራሱንም እንዳገያኝ ዝግ ማድረጉ ተገልጋዩ የሚፈልገውን አገልግሎት በወቅቱ እንዳያገኝ ማነቆ ሆኗል፡፡ በተመሳሳይ አለማዳመጥ ሌላው ችግር መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ የተቀመጠበት ወንበር ለኅብረተሰቡ አገልግሎት የመስጠት ግዴታ እንደሚጥልበት አለመቁጠርና ውሳኔንም በጊዜው አለመስጠት ኅብረተሰቡ ከሚያነሳቸው ችግሮች ዋነኞቹ ናቸው፡፡
እንደ አቶ የማነ ገለፃ፤ በአገልግሎት አሰጣጥ በከተማዋ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ከሁሉም በባሰ ደረጃ የሚነሳውና እስካሁንም ሙሉ በሙሉ ሊፈታ ያልቻለው የመሬት አጠቃቀም ጥያቄ ነው፡፡ በዋናነት ከዚህ ጋር በተያያዘ ከሲቪል ሰርቪሱና ነዋሪውም የሚያነሳው የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ነው፡፡ በዚህም ሁሉም በሊዝ ተወዳድሮ ማሸነፍ ስለማይችል ተደራሽነቱ ላይ ችግር የሚፈጥር በመሆኑ ተደራጅተው የመኖሪያ ቤት የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻች ይጠይቃሉ፡፡ መንግሥትም ጥያቄው ተገቢነት ያለው ሆኖ በማግኘቱ ከሞላ ጎደል እየመለሰው ሄዷል፡፡ በዚህም በ2009 በጀት ዓመት ብቻ ሲቪል ሰርቫንት፣ ነዋሪ እንዲሁም አካል ጉዳተኞችን ያካተቱ አንዱ ማህበር እስከ 24 ሰዎችን ላቀፉ 60 ማህበራት በየደረጃው በችግራቸው መጠን ተሰጥቷል፡፡ ይህም ይነሳ የነበረውን ችግር ሙሉ በሙሉ ይቀርፋል ማለት ባያስችልም ማቃለል ግን ተችሏል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ከተማው የካሳ መክፈያ ገንዘብ በማነሱ በዚያው ልክ የኅብረተሰቡን ጥያቄ ማስተናገድ አልተቻለም፡፡ ለተደራጁ 1 ሺህ 400 ወጣቶች የመኖሪያ ቦታ ለመስጠት ቢፈለግም የተጠየቀው ካሳ ግን 28 ሚሊዮን ብር በመሆኑና ይህም ከከተማው አቅም በላይ በመሆኑ ድህነቱ ያመጣው ችግር ጥያቄው እንዳይመለስ ጎታች ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡
በመሬት አጠቃቀም ላይ ፈጣን አለመሆን እንዲሁም መሐንዲሶች ላይ ኪራይ ሰብሳቢነት እንዳለ ኅብረተሰቡ በግልፅ ያነሳል፡፡ የከተማ አስተዳደሩም ቆራጥ ውሳኔ ወስኗል፡፡ በተሀድሶ መታደስ ያልቻለ ተቋም በማለት ተቋሙን ዳግም ከችግር ለማውጣት ሥራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ በዚህም ስድስት መሐንዲሶች ከነበሩበት እንዲነሱ፣ እንዲባረሩና በሕግ እንዲጠየቁ በተመሳሳይ በኃላፊነት ቦታ ላይ በነበሩ አመራሮች ፖለቲካዊ ውሳኔ አርፎባቸዋል፡፡ በዚህም ከኃላፊነት መነሳትን ጨምሮ ማስጠንቀቂያና ከነበሩበት ተነስተው በሌላ ቦታ ላይ እንዲመደቡም ተደርጓል፡፡ ይህም በቁርጠኝነት ኅብረተሰቡ የሚያነሳው ጥያቄ ትክክለኛነት በማመን በመሰራቱም የለውጥ ብርሃን ፍንጣቂ ማየት መቻሉን ይገልፃሉ፡፡
ከቀበሌና ከቀጣና የሚጀምሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ውስንነቶች መኖራቸውን የሚገልፁት የሕዝብ ግንኙነት መኮንኑ ከስኳርና ዘይት ማከፋፈል እንዲሁም መታወቂያ አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ውስንነቶች መኖራቸውን ይገልፃሉ፡፡ ይሁን እንጂ አስተዳደሩ ከነዋሪው ጋር ባለው ጥብቅ ግንኙነት የሚነሱ ችግሮችን ከስር ከስር እንዲፈቱ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ውሃና መብራት በሰፊው ችግሮች የሚነሱባቸው ዘርፎች ናቸው፡፡ ተቋማቱ የሚሰጡት አገልግሎት ጥራትና ብቁነት እንደሚጎድላቸው ይነሳል፡፡
በመብራት ዙሪያ በምሬት ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸው ችግሮች በመኖራቸው ወደ ኅብረተሰቡ በመውረድና በማነጋገር በሰራው ሥራ ለውጥ መጥቷል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ከአቅም በላይ የሆኑ ችግሮች እንዳሉ ኅብረተሰቡ ተገንዝቧል፡፡ ይህም የትራንስፎርመር ችግር መንግሥት ሊፈታው ያልቻለው መሆኑ ለእርሳቸውም ግራ እንደሚሆንባቸው አቶ የማነ ይናገራሉ፡፡ በአገር ውስጥ ለመብራት የሚሆን በቂ ኃይል አለ ሲባል ቢሰማም ችግሩ ግን ሊፈታ ያልተቻለበት አጥጋቢ ምክንያት ለኅብረተሰቡ መናገር ያልቻለ ተቋምም መብራት ኃይል ነው ይላሉ፡፡ በከተማዋ 25 ሺህ አባወራዎች የመብራትም ሆነ የውሃ ስርጭት የሌላቸው ናቸው፡፡ ይህም በከተማ ነዋሪ የሆነ ዜጋ ማግኘት ያለበት አገልግሎት ቢሆንም ከተማን ከተማ የሚያስመስል አገልግሎት እያገኙ አለመሆናቸውን ይጠቁማሉ፡፡
የጠጠር መንገዶች ዝርጋታ የውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ የመሳሰሉ ከችግር የተነሱ መፍትሄዎችን ኅብረተሰቡ በራሱ ጉልበት እየቆፈረ መንግሥት ቀሪውን ድጋፍ እንዲያደርግ እየሰራ ነው፡፡ ይህን መሰል የነቃ የኅብረተሰብ ተሳትፎ መኖሩም ልማቱን ከማፋጠን ባሻገር የባለቤትነት መንፈስን የሚያዳብር በመሆኑ በቀጣይም እዚህ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል፡፡
እንደ ሕዝብ ግንኙነት መኮንኑ ገለፃ፤ ፍትህ ማስፈንን በተመለከተ በከተማዋ በተለይ ከሴቶች ጥቃት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮች አሉ፡፡ ምንም እንኳን ሴቶች ለዚህ ሰላምና ዴሞክራሲ ከወንዶች እኩል የሕይወትና የአካል መስዋዕትነት ቢከፍሉም አሁንም ግን በማህበራዊ ፆታ የተነሳ እኩል ካለመታየት አልፎ ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ሲደርስባቸው ገና በለጋ ዕድሜያቸውም የመደፈር አደጋ ሲደርስባቸው ይታያል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ከ 10 በላይ ሴቶች በሕግ የተያዘ ጉዳይ አላቸው፡፡ ነገር ግን የሕግ ተፈፃሚነት እና ቅጣት አወሳሰን ላይ ተገቢና ፈጣን ብይን አይሰጥም የሚሉ ትችቶች ይሰነዘራሉ፡፡ በጉዳዩ ላይም የፍትህ አካላት ችግሩ ከመከሰቱ አስቀድሞ ግንዛቤ መፍጠር ላይ ችግር ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅትም ይህን ለማቃለል ተቀራርቦ መስራት ላይ እየመጡ ያሉ ለውጦች አሉ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ኅብረተሰቡ «ሰላሜን እኔ ማስከበር ካልቻልኩ ማን ሊያስከብርልኝ ይችላል» በሚል በራሱ ገንዘብ እያዋጣ ማህበረሰብ አቀፍ ፎረሞችን እየገነባ ይገኛል፡፡
የልማት ሥራዎች
ከተማዋ ያላት መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ በተራራ የተከበበች በመሆኑ ለጎርፍና ተያያዥ ችግሮች ተጋላጭ አድርጓት ቆይቷል፡፡ ምንም እንኳን ለኑሮ ምቹ ብትሆንም በጎርፍ ግን በርካታ ጊዜያትን በጉዳት አሳልፋለች፡፡ የከተማ አስተዳደሩም የጎርፍ መከላከያ ግንባታዎችን ማካሄድ አቅም ያንሰዋል፡፡ ኅብረተሰቡም ከተማዋ ይሄን ያክል በጎርፍ ስትጎዳ የክልሉና የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ አለማድረጋቸው ላይ ትችት ያቀርባል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ለዚሁ ችግር ማቃለያ የሚሆን በየዓመቱ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ለጎርፍ ማስወገጃ ቱቦዎች ይመድባል፡፡ ኅብረተሰቡም በዚያው ልክ ከአምስት እስከ ሰባት ሚሊዮን ብር በላይ በገንዘብ፣ በጉልበቱና በእውቀቱ ይደግፋል፡፡ በዚህም በየዓመቱ አንድ ኪሎሜትር ያክል ቁፋሮ ይሰራል፡፡
የከተማው ነዋሪ በሚያነሳው የመልማት ጥያቄዎች ውስጥ ከሚታዩት መልካም አስተዳደር ችግር መካከል የውሃ ጥያቄ ይገኝበታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ጊዜያዊ መፍትሄ ያግኝ እንጂ በቅርቡ ከተማዋን የውሃ ችግር ክፉኛ መቷት እንደነበር አቶ የማነ ያስታውሳሉ፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ ባልታሰበ ሁኔታ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ 11 የውሃ ጥልቅ ጉድጓዶች ደርቀው ሰባት ብቻ ቀሩ፡፡ ባጋጠመው አደጋም ሕዝቡ ተደናግጦ ነበር ይላሉ፡፡ ችግሩም የጉድጓድ ውሃ አስተማማኝ አለመሆኑን አስተምሮ አልፏል፡፡ ለዚህም ግንባታው ቢንጓተትም ጊዜያዊ መፍትሄ ተደርጎ የተወሰደው አውሮፓ ህብረት በመደበው 126 ሚሊዮን 15 ጉድጓዶችን ተቆፍረው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ በዚህም በአሁኑ ወቅት ከገጠር ወደ ከተማ የገቡት የቧንቧ ዝርጋት ውስንነት ላይ የሚነሳ ችግር ካልሆነ በቀር አቅርቦቱ ላይ ከሞላ ጎደል መሻሻሎች ታይተዋል፡፡ ኅብረተሰቡ የሚጠይቀውን ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣትም በሌሎች አካባቢዎች እንደተሰራው በከተማዋ ትልቅ ግድብ መሰራት ይኖርበታል አልያ ግን ከዚህ ቀደም ተከስቶ የነበረው ዓይነት ችግር ላለመከሰቱ ዋስትና የለም ባይ ናቸው፡፡
ቀድሞ 30 ሺህ ሕዝብ በነበረበት ወቅት አገልግሎት እንዲሰጥ ለምሥራቃዊ ዞንና ለከተማው የተሰራው ሪፈራል ሆስፒታልም ባለበት መቆሙ አሁን እያደገ የመጣውን የከተማዋን ነዋሪ የማይመጥን ነው የሚለው ችግር ሌላው የኅብረተሰብ ጥያቄ ነው፡፡ አገልግሎት አሰጣጡም በዚያው ልክ ችግር እንዳለበት ይነሳል፡፡ በዚህም ኅብረተሰቡ ሌሎች አማራጮችን ፍለጋ በመሄድ ለአላስፈላጊ ወጪ እየተዳረገ ይገኛል፡፡ ዓዲግራት ዪኒቨርሲቲ ለሪፈራል ሆስፒታሉ 30 ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ ግንባታ እያካሄደ ቢሆንም ለዘላቂ መፍትሄ ግን መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ለነዋሪው የሚመጥን አገልግሎት እንዲሰጥ መስራት አለበት የሚሉ አስተያየቶች ኅብረተሰቡ ያነሳል፡፡
ሥራ ዕድል ፈጠራ
በከተማዋ በአምስቱ ዕድገት ዘርፎች ለሌሎች ተሞክሮ የሚሆን ሥራ ይሰራ እንደነበር አቶ የማነ ያስታውሳሉ፡፡ ነገር ግን ከዓለም ባንክ ከተማ ልማት ፕሮግራም ለወጣቶች ይቀርብ የነበረው ተዘዋዋሪ ፈንድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መሄዱ አሉታዊ አስተዋፅዖ አበርክቷል፡፡ በዚህም ወጣቱ የሚፈልገውን ያክል ብድር መጠን ማግኘት አለመቻሉ የሥራ ተነሳሽነቱን ቀንሶታል፡፡ ይህም ከሥራ ይልቅ በወጣቱ ላይ ያልተለመዱ ባህርያት በሱስ መጠመዶችን እያመጣ ነው፡፡ ነገር ግን በሌላ በኩል ደግሞ በተፈጠረው የሥራ ዕድል ተሰማርተው ውጤት ማስመዝገብ የቻሉ በርካቶች ናቸው፡፡ በዚህም የራሳቸውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባሻገር ለሌሎችም የሥራ ዕድል መፍጠር የቻሉና ሀብት ፈጥረው ደረጃቸውን እያሳደጉም መሄድ የቻሉ አርአያ ወጣቶች ይገኛሉ፡፡
መንግሥት ለሚደራጁ ወጣቶች ከሼዶች ጀምሮ አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ከጥቃቅንና አነስተኛ በመነሳት ወደ ባለሀብትነት እንዲሸጋገሩ ይደግፋል፡፡ ለአብነት ከዚህ ቀደም በከተማዋ ቆሻሻ የነበሩ አካባቢዎችን ወደ አረንጓዴ ልማት ቀይረው መንፈስ ማደሻ ያደረጉ ወጣቶች ይገኛሉ፡፡ በሌላ በኩል በክልሉ አስተዳደርና በወጣቶቹ ከሚፈጠረው የሥራ ዕድል በተጨማሪ ከፌዴራል የተመደበው ተዘዋዋሪ ፈንድ በሳምንት ጊዜ ውስጥ አልቋል፡፡ ይህ የሚያመላክተውም የከተማዋ ወጣቶች መንገድ ከተመቻቸላቸው ያላቸው የሥራ ፍላጎት የናረ መሆኑን ነው ይላሉ፡፡
ወጣቶች ለሚያነሷቸው የብድር አቅርቦት እጥረትና የሥልጠና ዘርፎች ውስንነት ችግር የሕዝብ ግንኙነት መኮንኑ ምላሻቸውን ሲሰጡ በከተማዋ በኮብልስቶን የሚፈጠረው የሥራ ዕድል መሸጋገሪያ ድልድይ እንጂ ዘላቂ እንዲሆን አይጠበቅም፡፡ ነገር ግን ከዚህ ጋር በተያያዘ የግንዛቤ ፈጠራ ላይ የሚታዩ ውስንነቶች አሉ፡፡ በሥራቸው 20 ሺህ መቆጠብ ከቻሉ ያችን ይዘው ከደደቢት ብድርና ቁጠባ ተቋም 100 ሺህ በመበደር ወደ ቋሚ ሌላ ሥራ ሽግግር እንዲያደርጉ ደጋፊ ድልድይ ነው፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይ በሚፈለገው ደረጃ በአስተሳሰብ ላይ ባለመሰራቱ የሚጠበቀውን ለውጥ ላይመጣ ችሏል፡፡
ኃላፊነትንና ተጠያቂነት
እንደ አቶ የማነ ገለፃ፤ መንግሥት ባወጣው የተለያዩ ፖሊሲና ስትራጂዎች ላይ ተቃውሞ ሲነሳ ባይሰማም ይህንን መሬት ላይ ወርዶ ተፈፃሚ እንዲሆን ከማድረግ ጋር ተያይዞ ግን ችግሮች ይታያሉ፡፡ በእርግጥ በሥራ ውስጥ ሁሌም ቢሆን የሚታዩ ችግሮች ቢኖሩም በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ የተነሳበት ሕዝባዊነት ስሜት እየተሸረሸረና ሕዝበኛነቱ እየነገሰ መጥቷል፡፡ በዚህም የሰላምና ደህንነት እንዲሁም በብዝሃነት ላይ ያንዣበቡ ችግሮችም ይታያሉ፡፡ ለዚህ ችግርም እንደ ዋነኛ መንስኤ የሚሆነው ቀድሞ ለዚህ ሥርዓት መምጣት መሠረት የነበረው ጭቆናዊ አገዛዝ መገርሰስ ቁርሾ ያለባቸው አካላት ዛሬም የአገሪቱን ማደግ ሳይሆን የግል ክብራቸውን ለማስጠበቅ በአገርም በውጪም ሆነው መራወጣቸው መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ቀድሞ ተሸናፊ የነበረው አካል ዛሬ አገሪቱን አጥፍቶ ሊጠፋ ይፈልጋል፡፡ በዚህም የአገሪቱን መልማት ከማይፈልጉ አካላት ጋር ለጥፋት በመቀናጀት አንበሳ ገዳይነቱን ሊያሳይ የሚፈልግ ኃይል አለ፡፡
ችግሩ የሚፈጠረውም ለሰላምና ለዴሞክራሲ በተከፈለው መስዋዕትነት ምክንያት በወቅቱ ያኮረፉና የግል ጥቅማቸው የቀረባቸው አካላት እያመጡት ያለ ነው፡፡ ቀጣይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለመልካም አስተዳደር በርካታ ትሩፋቶችን ያመጣል ተብሎ የሚጠበቀው የታላቁ ህዳሴ ግድብ እንዳይገነባ ያላቸውን ጥልቅ ፍላጎት በተለያየ መንገድ ሲያንፀባቁም ይስተዋላል፡፡ ይህም ከአገራዊ ስሜት ፍፁም የራቀ እኩይ አመለካከትና ተግባር መሆኑንም መገንዘብ ይገባል፡፡ በውስጡም በአስተሳሰብ ያልበሰሉ ወጣቶች በመያዙ አገሪቱን እያተራመሱ መንግሥት መምራት አትችልም የሚሉ ሀሳቦች ሲነሱ ይሰማል፡፡
እነዚህ ጠላቶች ስር ሰደው ይህንን የሚቋቋምና አስተሳሰቡን የሚሸከም ትውልድ እስኪፈጠር ምን እየሰራ ነበር? የሚል እንዲሁም ይህንን መመከት የሚችል አስተሳሰብ መፍጠር ላይም መንግሥት እንዳልሰራ ታይቷል፡፡ ይህም ለጥፋት ኃይሉ ምቹ ማዳበሪያ የሆነ አመራር እንዳለ አመላክቷል፡፡ ይህንንም መሠረት ተደርጎ በየደረጃው ጥልቅ ተሃድሶ እየተካሄደ ነው፡፡ ይህም ፍፁም የማጥራት ሥራን ማዕከል ያደረገ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ገና ከአሁኑ በጎ አስተያየቶችን እየሰጠ ይገኛል በማለት ችግሮቹን ለማቃለል ወደ ውስጡ ማየቱ ለውጥን እንደሚያመጣ ያላቸውን ዕምነት ይናገራሉ፡፡
ቀጣይ
በቀጣይ በአሁኑ ወቅት በየደረጃው እየተካሄደ ባለው ጥልቅ ተሃድሶ መሠረት በተሰጠው አቅጣጫ ሕዝቡን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎች መስራት ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ ችግሮችንም በምን ዓይነት መልኩ ሊፈቱ እንደሚገባቸው በትኩረትና በጥልቀት ይቀመጣል፡፡ በዚህም የኅብረተሰቡን ተሳትፎ ባማከለ መልኩ የሕዝቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ልማት ለማስመዝገብ እንደሚሰራ አቶ የማነ ይገልፃሉ፡፡
ሚኒስቴሩ
በከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የኅብረተሰብ ተሳትፎና ያልተማከለ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ መንግስተኣብ ተክሉ እንደሚናገሩት፤ በከተማዋ የነቃ የኅብረተሰብ ተሳትፎ እንዳለ በሚኒስቴሩ ተለይቷል፡፡ በተጨባጭም ከዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የመጡ አካላትም ታች ድረስ ወርደው ሥራውን ተመልክተዋል፡፡ ወደየራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ወስደው ተግባራዊ እንደሚያደርጉ እንደሚያሰፉ ዝግጁ መሆናቸውን መረዳት ተችሏል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ ኅብረተሰቡ በዚህ ደረጃ ተሳትፎ ማድረጉ እጅ ከመጠቆም ባለፈ በሥራው በባለቤትነት እንዲሳተፍ ስለሚያደርገው የመልካም አስተዳደር ችግሮችንም እንዲቃለሉ ያግዛል፡፡ በዚህም አላስፈላጊ ድርጊቶች ተፈፅመው ሲመለከት ራሱ ያጋልጣል ለችግሮችም መፍትሄ ያመጣል፡፡ የሚሰጠው አገልግሎትም በጊዜው በጥራት የተሻለ እንዲሆን በማድረግ የሚነሱ ችግሮችን መጠን በሰፊው ያቃልላል፡፡ የተሰሩ ልማቶችን ከማውደምና ከመከላከል ባሻገር ልማቱ የራሱ በመሆኑ ከሥራው ስር መሠረት ጀምሮ በሚፈለገው ጥራት እንዲሰራ ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም ዘላቂ የሆነ ልማት እንዲመጣ የኅብረተሰብ ተሳትፎ ያስፈልጋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እየወደሙ ያሉት ልማቶች ምንም እንኳን ሌላ ድብቅ አጀንዳ ያላቸው አካላት እጅ ከበስተጀርባ ቢኖርበትም የሚሳተፈው በተለያዩ ችግሮች ብሶት ያለበት ወጣት ነው፡፡ ለዚህም የይስሙላ፣ አስመሳይና ጥገኛ አመራር መሰብሰቡ ተጠቃሽ ምክንያት ይሆናል፡፡ ለሕዝብና መንግሥት መራራቅ አስተዋፅዖ ለማበርከታቸው ተጠያቂ የሚሆነውም መንግሥት ነው፡፡
ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው ወጥተው ሥራ ያላገኙ ወጣቶች ሌሎች ከኋላ ሲገፏቸው ወደ ጥፋት የማይገቡበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ይህንንም መቀልበስ የማይችል አመራር ካለ ችግሮች መስፋታቸው አይቀርም፡፡ «መንግሥት መታገስ እንጂ መልፈስፈስ የለበትም» የሚለውን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ አባባል በማስታወስ አመራሩ የተቀመጠበትን ዓላማ አውቆና ተረድቶ ሕዝቡን ማገልገል እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ ለዚህም መፍትሄ የሚሆነው የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ልማቱን እንዲጠብቅና በአገር ደረጃ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ ዕድገቶችን ለማስመዝገብ የተያዙ አጀንዳዎችን ለማሳካት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ዳይሬክተሩ ያመላክታሉ፡፡

ፍዮሪ ተወልደ

Published in ፖለቲካ

በኢትዮጵያ የኅብረት ሥራ ማህበራት ታሪክ 50 ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ማህበራቱ በሥርዓት ተደራጅተው፤ በፖሊሲ ታቅፈው ሥራ ከጀመሩ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ አልሆናቸውም፡፡ በአሁኑ ሰዓት የግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመርና ወደ ውጭ በመላክ ለአገሪቷ ገቢ ያስገባሉ፡፡ የኅብረት ሥራ ማህበር ኤጀንሲ የኅብረት ማህበራትን እንቅስቃሴ የማጎልበት፣ የሰው ኃይል የማሰልጠን፣ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀርፆ የማቅረብ፣ የጥናትና ምርምር ተግባራትን የማካሄድ ኃላፊነት ተሰጥቶት በአዋጅ ቁጥር 274/94 የተቋቋመ መስሪያ ቤት ነው፡፡ በዚህም በአገሪቱ ውስጥ የህብረት ስራ ማህበራት ድህነትና ኋላቀርነትን ከአገሪቱ ለማስወገድ የተነደፉ የልማት ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና እቅዶች እውን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
የኅብረት ሥራ ማህበራት ከዘይት፣ ስኳርና ዱቄት በተጨማሪ በርካታ የግብርና ምርቶችን ለተጠቃሚው ያቀርባሉ፡፡ ያም ሆኖ ግን መንግሥት በድጎማ የሚያቀርባቸው እነዚህ ምርቶች ላይ የአቅርቦትና የፍላጎት ያለመጣጣም ችግር አለ፡፡ ስለሆነም አነስተኛ ገቢ ላለው ኅብረተሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ በማህበራት አማካይነት ያቀርባል፡፡ በመዲናዋ ከ130 የሚበልጡ ማህበራት አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ጥቂቶቹ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባራት እንደሚስተዋልባቸውና እነዚህንም ተከታትሎ እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ የኅብረት ሥራ ማህበር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር ይናገራሉ፡፡
የኅብረት ሥራ ማህበራት የአርሶና አርብቶ አደሩን ምርት ለማሳደግ የሚያስችሉ የምርት ግብአቶችን በማቅረብና የተሻለ ገበያ ዋጋ በመፈለግ የአርሶና አርብቶ አደሩን ኑሮ በመለወጥ በከተማና በገጠር የሚኖረውን ኅብረተሰብ የቁጠባ ባህል ከማዳበሩም በዘለለ ለኅብረተሰቡ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የዋጋ ንረትን ለማርገብ የኅብረት ሥራ ማህበራት የጎላ ሚና እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ አልፎ አልፎ በሚከሰተው የዋጋ ንረት ምክንያትም መሠረታዊ ፍጆታዎች ኅብረተሰቡ እያገኘ አለመሆኑን ይነገራል፡፡ የሸማች ኅብረት ሥራ ማህበራትም መሠረታዊ ፍጆታዎች በተፈለገው መጠን ከኅብረት ሥራ ማህበራት እየቀረቡለት አለመሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
ማህበራቱ ለረጅም ጊዜ በሙስና መረብ ተጠልፈው ቆይተዋል። በአሁኑ ወቅት ግን የኅብረት ሥራ ማህበራት ከተቋቋመላቸው ዓላማ አኳያ ሕዝቡን እንዲያገለግሉና አባላቱን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ መንግሥት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው። የኅብረት ሥራ ማህበራት ዓላማቸው የሸማቾችን ፍላጎት ማሟላትና የኑሮ ውድነትን መቀነስ ነው ተብሎ ቢታሰብም በአዲስ አበባና አንዳንድ የአገራችን ክልሎች የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበራት ላይ የሸቀጦች ሽያጭ የሚካሄደው በቀበሌ መታወቂያ አማካኝነት ነው። ይህ ደግሞ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተደራሽ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡
የኅብረት ሥራ ማህበራት የአባላትን ኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያደርጉት የሥራ እንቅስቃሴ በየጊዜው እያደገ ይገኛል፡፡ ዘርፉን ለማጠናከር በተሰራው ሥራ ከ17 ሚሊዮን በላይ አባላት ያፈሩ ከ83 ሺ በላይ መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማህበራት፣ 381 የኅብረት ሥራ ዩኒየኖች እና ሦስት ክልላዊ የኅብረት ሥራ ፌዴሬሽኖች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተደራጅተው 20 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ካፒታል ማፍራትና 13 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ቁጠባ በማሰባሰብ ለአገሪቱ እድገት አስተዋፅኦ እያደረጉ እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ኡስማን ሱሩር ይናገራሉ፡፡
በግብርናው ዘርፍ የተደራጁ ኅብረት ሥራ ማህበራት የአርሶና የአርብቶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በዘላቂነት ሊያሳድጉ የሚችሉት ለተመረተው ምርት በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም ገበያ መዳረሻቸውን በማስፋት ለአምራቹ ምርት ተመጣጣኝና ፍትሐዊ የገበያ ዋጋ ማግኘት እንዲችል ሲያደርጉ መሆኑን አቶ ኡስማን ይናገራሉ፡፡ ይህን ለማሳካት የኅብረት ሥራ ማህበራቱ የገበያ መዳረሻቸውን በአገር ውስጥና በውጭ አገራት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ከኅብረት ሥራ ማህበራቱ መዳረሻዎች መካከል በዋነኝነት በከተሞች የሚገኙ ሸማች ኅብረት ሥራ ማህበራት፣ የግብርና ምርቶች የሚያቀናብሩ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም ለአደጋ ጊዜ የግብርና ምርቶችን ከሚያከማቹ ተቋማት ጋር የሚደረጉ ትስስሮች ተጠቃሾች መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡
በኅብረት ሥራ ማህበራትና በመሠረታዊ ሸማች ኅብረት ሥራ ማህበራት መካከል ትስስር በመፍጠር ኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የግብርና ምርቶችን እንዲያገኝ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንና የኅብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒየኖች የግብርና ምርቶች ማቅረብ ላይ ያሉባቸውን ችግሮች በመፍታት ምርቶችን ለኅብረተሰቡ እንዲያቀርቡ ለማድረግ ኤጀንሲው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ኃላፊው ይገልፃሉ፡፡ በመሠረታዊ ሸማች ማህበራት ሲቋቋሙ በዋናነት ገበያ የማረጋጋት ሥራ ሊሰሩ እንደመሆኑ በግብርና ምርቶች ላይ የዋጋ መናር ሲፈጠር ከኅብረት ሥራ ማህበራት ጋር በመተባበር የዋጋ ማረጋጋት ሥራ እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ በዚህም ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ያስረዳሉ፡፡
የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ የግብይት ዳይሬክተር አቶ ሙሉሻው በቀለ፤ በአገሪቱ የዋጋ መናር ሲከሰት መሠረታዊ ሸቀጦችን መሠረታዊ ሸማች ማህበራቱ በራሳቸው የሚያመጡትበት ሁኔታ አለ፤ የግብርና ምርት ደግሞ ከኅብረት ሥራ ከዩኒየኖች እንደሚረከቡ ይናገራሉ፡፡ መሠረታዊ ሸማች ኅብረት ሥራ ማህበሩ ከተመደቡለት ዩኒየኖች የግብርና ምርቶችን የሚያስገባ ሲሆን፣ በዩኒየኖቹ የማይገኙ ምርቶችን ደግሞ ከክልል አምራች ማህበራት ጋር ትስስር በመፍጠር ምርት በማስገባት ለመሠረታዊ ሸማች ማህበራት ያስረክባሉ፡፡ የምርቶቹ ብዛትና የሚመጡበት ጊዜ የሚወሰነው መሠረታዊ ማህበሩ በሚያቀርበው ጥያቄ መሠረት ነው፡፡ መሠረታዊ ሸማች ማህበሩ በማንኛውም ሰዓት ምርት እንዲቀርብለት ጥያቄ ሲያቀርብ የኅብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒየኖች የማቅረብ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
በአስሩም ክፍለከተሞች ምርት የሚያቀርቡ የተመደቡ ዩኒየኖች አሉ፡፡ ዩኒየኖቹ በሥራቸው ላለው መሠረታዊ ሸማች ማህበር ምርት ያቀርባሉ፡፡ መሠረታዊ ሸማች ማህበሩ አተር፣ ስንዴ፣ ባቄላና ጤፍ ይህን ያክል ኩንታል ብሎ ሲያሳውቅ ምርቶቹ በፍጥነት እንደሚቀርቡ ያመለክታሉ፡፡ ዩኒየኖቹ የገበያ መጨመር ቢከሰት እንኳን ቀድሞ ሲያቀርቡበት በነበረው ዋጋ እንጂ ጭማሪ እንደማያደርጉ የሚጠቅሱት አቶ ሙሉሻው፤ በምሳሌነትም በጥር ወር ላይ የተገዛው ምርት የካቲት ወር ላይ መጨመር ቢያሳይ ከዩኒየኖቹ ማቅረቢያ ዋጋ እንደማይጨምር ይጠቁማሉ፡፡ ምርቶችን ለመሸጥ ቀድሞ በተተመነው ዋጋ ነው የሚሸጠው፡፡ ይህም የዋጋ መጨመር ሲከሰት ለማረጋጋት በሚደረጉ ሥራዎች አጋዥ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
በመሠረታዊ የሸማች ኅብረት ሥራ ማህበራት ያሉት ችግሮች በዋነኝነት በተገቢው መልኩ ለኅብረተሰቡ የሚፈልገውን ምርት አውቀው ለዩኒየኖች ምርት እንዲመጣላቸው ጥያቄ እንደማያቀርቡና እዚህ ላይ ክፍተት እንዳለ ይጠቁማሉ፡፡ ይህን ደግሞ በቀጣይ የማስተካከልና የማረም ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እየተሰራ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አዲስ አደረጃጀት በመፍጠር እስከ ወረዳ ድረስ የኅብረት ሥራ ማህበር የሚያጠናክሩ ጽሕፈት ቤቶች ተከፍተዋል፡፡ ጽሕፈት ቤቶቹ ደግሞ በየመሠረታዊ ሸማች ማህበሩ የግብርና ምርቶች ሕዝቡ በሚፈልገው መልኩ መኖር አለመኖራቸውን ይቆጣጠራል፡፡ ስለዚህ በቀጣይ ሁሉም ጋር እኩል የግብርና ምርቶች ተደራሽ የሚሆኑበት ዕድል እየፈጠረ እንደሚገኝ ያመለክታሉ፡፡
እንደ አቶ ሙሉሻው አባባል፤ ከዩኒየኖች የሚመጣው ምርት በቀጥታ ለኅብረተሰቡ እንዲደርስ ይፈለጋል፡፡ ማንኛውም ሰው ምርቱን ሄዶ ማግኘት ይችላል፡፡ አብዛኛው ምርቶች በመጋዘን ውስጥ ቢኖሩም ሰው እንዲገዛ የማድረግ ሥራ አናሳ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ አካባቢ ያሉት ችግሮች እንዲቀረፉ የጤፍ ዘሮችን በየዓይነታቸው ስም ተፅፎበት በኪሎ በየሱቁ እንዲሸጥ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ቀደም ብሎ ኅብረተሰቡ በወፍጮ ቤቱ ብቻ ነበር ጤፍ ገዝቶና አስፈጭቶ የሚጠቀመው፡፡ አሁን ግን ይህን ባህል ለመቀየር ኅብረተሰቡ የሚፈልገውን ያክል የተፈጨ ጤፍ መግዛት እንዲችል ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ያመለክታሉ፡፡
በአጠቃላይ የኅብረት ሥራ ማህበራት ገበያን ለማረጋጋትና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የሚጫወቱት ሚና የላቀ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን ዘርፉ እስከታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ድረስ ወርዶ የሚሰጡ የአገልግሎቶች ላይ የሚታዩ ችግሮችን መፈተሽ ይጠበቅበታል፡፡ ምክንያቱም ኅብረተሰቡ በሸማቾችና ዩኒየኖች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግሮች እንዳሉ በተደጋጋሚ ሲያነሳ ይሰማል፡፡ ስለዚህ የኅብረት ሥራ ማህበሩ የያዘውን ዓላማ እንዲያሳካ ከኅብረተሰቡ ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከርና በውስጥ የሚታዩ የአሠራር ክፍተቶችንም ፈትሾ ማስተካከል ይጠበቅበታል፡፡

መርድ ክፍሉ

Published in ኢኮኖሚ

የዓረብ ፀደይ ሰባተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ወቅቱ እ.አ.አ. 2011 ነው፡፡ _በዓረብ አገሮች አዲስ ክስተት የተባለለት ሕዝባዊ አመፅ ተቀሰቀሰ፡፡ ለበርካታ ዘመናት በመንበረ ሥልጣናቸው ቤተ መንግሥት የማያስነኩት የዓረብ ንጉሣዊ ቤተሰቦችና መንግሥታት ሥፍራቸውን እንዲለቁ ሕዝባቸው ቀጥተኛ ጥሪ አስተላለፈ፡፡ ለጥሪው የመንግሥታቱ ምላሽ አገሮቹን ወደ መቀመቅ ከተተ፡፡ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የተጀመሩ ሰላማዊ ሠልፎች ወደ አመፅ ተቀየሩ፡፡
መንግሥታቱ የታጠቁትን መሣሪያ ወደ ሕዝብ አዞሩ፣ ሕዝብን የወገኑ የመንግሥት ወታደሮችም ከሕዝብ ጎን ተሠልፈው ወደ እርስ በርስ ጦርነት ገቡ፡፡ አጋጣሚውን ተገን በማድረግ በየአገሮቹ የውስጥና የውጭ ኃይላትም እጃቸውን አስገቡ፡፡ ጦርነቶቹ የእርስ በርስ፣ ቅዱስ ጦርነት፣ እንዲሁም የቀዝቃዛ ጦርነት መልክ መያዝ ጀመሩ፡፡ ለአንድ ወጥ ዓላማ የሚደረግ አንድ ዓይነትና ተለምዶዓዊ ጦርነት የሚባል ነገር ጠፋ፡፡ በጦርነት ላይ የተሰማሩት አካላት ጠላታቸውን ከወዳጆቻቸው መለየት እስኪሳናቸው ግራ ተጋቡ፡፡ በዚህም የበርካታ ንፁሃን ዜጎች ሕይወት እንደ ቅጠል ረገፈ፡፡ ለተካሄዱ አብዮቶች መነሻ የነበሩ ሁኔታዎች ግን ሳይለወጡ ቀጠሉ፡፡ አብዮቶቹ የተቀሰቀሱባቸው አገሮች ቀደም ሲል የነበራቸውን መረጋጋትና ሰላም ማስመለስ ተሳናቸው፡፡
በሶሪያ ጦርነት ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆኑ ቢያንስ ሦስት አካላት ይገኛሉ፡፡ እነዚህም በፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ የሚመራው የመንግሥት ጦር፣ የአማፅያን ጎራ፣ የኩርዶች ቡድን ናቸው፡፡ ሁሉም የየራሳቸውን ዓላማ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ የበሽርን አስተዳደር ከሥልጣን ለማውረድ ወደ ፍልሚያ የገባው የመጀመሪያው የመንግሥት አማፂ ቡድን ከመንግሥት ጦር እየከዱ ከነትጥቃቸው በሚኮበልሉ አባላት እየተደራጀና እየተጠናከረ፣ ቀደም ሲል በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የነበሩ ሥፍራዎችን እያስለቀቀ ግስጋሴውን ቀጠለ፡፡
በዚህም ግስጋሴ የዓለም ሚዲያዎች የበሽር አስተዳደር ፍፃሜ መቃረቡን መዘገብ ጀመሩ፡፡ ከአማፅያኑ ጎን ተሠልፈው የሚዋጉት ኩርዶችና ከኢራቁ የአልቃይዳ ክንፍ ክፍፍል በመፍጠር ተገንጥሎ ወደ ሶሪያ የገባው አይኤስ አንደኛው የሌላኛው ጠላት በመሆን ትኩረታቸውን ከጅምር እንዳደረጉት ሙሉ ኃይላቸውን በመጠቀም መንግሥትን ከመፋለም ይልቅ፣ አንደኛው የሌላኛው ጠላት በመሆን የእርስ በርስ ፍልሚያ ውስጥ ገብተው ሰነባብተዋል፡፡ ሆኖም በአንድ በኩል መንግሥትን በሌላ በኩል ደግሞ እርስ በርስ ፍጅታቸውን ቀጠሉ ፡፡
በአሁኑ ወቅት በአውሮፓና በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ የሚገኙ ባለሥልጣናት በጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ ሶሪያውያን ወደ አገራቸው በሚመለሱበት ሁኔታ ላይ እየተከራከሩ ይገኛሉ፡፡ በየመጠለያው ጣቢያው የተጠፋፉ ቤተሰቦችን አገናኝቶ ወደ አገራቸው የመመለስ ሂደትም በባለሥልጣናቱ ትከሻ ላይ የተጫነ ሥራ ነው ሲል አልጀዚራ በድረገፁ አስነብቧል፡፡
የመንግሥት ባለሥልጣናትም ከአገሪቱ በቅርብ ርቀት በሚገኝ ቢሯቸው ውስጥ ሆነው የሚወስኗቸው ደካማና ትኩረት የጎደለው ውሳኔያቸው በአደጋ ላይ የሚገኘውንና ባለበት ሁኔታ ወደ አገሩ የሚመለሰውን የሀገሪቱን ነዋሪዎች ሃሳብ የያዘ አይደለም፡፡ ይህም ሁኔታ በስቃይ ላይ የምትገኘውን ሶሪያ ወደ ባሰ ሁኔታ ሊወስዳት እንደሚችል ዘገባው ይጠቅሳል፡፡
ለሰባት ዓመታት የዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት በነዋሪዎቹ ላይ ከፍተኛ ስቃይ ፈጥሯል፡፡ በዚህም የአገሪቱ ግማሽ ያህል ሕዝብ ወደሌሎች አገራት ተሰዷል፡፡ ከስድስት ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች በሶሪያ ውስጥ ከነበሩበት ተፈናቅለዋል፡፡ አምስት ሚሊዮን ሕዝብ ደግሞ በጎረቤት አገራትና ወደ አውሮፓ በስደት በጥገኝነት እየኖረ እንደሚገኝ ዘገባው ያሳያል፡፡
የኖርዌይ ምክር ቤት የሶሪያን ስደተኞች ባናገረበት ወቅት አብዛኛው ስደተኛ ወደ አውሮፓና አሜሪካ መሄድ አይፈልጉም፡፡ ጆርዳን፣ ሊባኖስና ቱርክ ድንበራቸውን ክፍት በማድረግ ለመቀበል ዝግጁ ቢሆኑም ስደተኞቹ በእነዚህ አገራት የመቆየት ፍላጎት የላቸውም፡፡ የስደተኞቹ ፍላጎት ወደ አገራቸው መመለስ ሲሆን ይህም በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት ቢሆን ፍላጎታቸው መሆኑን ዘገባው ያብራራል፡፡
ነገር ግን በሶሪያ ውስጥ የሚገኙ ተቃዋሚዎች እርስ በርስ እየተዋጉ ይገኛሉ፡፡በአገሪቱ ሰሜንደቡብ አካባቢ በተደረገው ጦርነት ሩብ ሚሊዮን ሕዝብ ተፈናቅሏል፡፡ ይህም የሚያሳየው በአካባቢው ብዙ ሚሊዮን ሰዎች እየተሰደዱ እንደሚገኙ ነው፡፡ በተጨማሪም በደቡብ በምሥራቅ ጉትዋ አካባቢዎች የሚኖሩ 400ሺ ነዋሪዎች ለረሃብ ተጋልጠዋል፡፡ በሁሉም የጦር ቀጣና አካባቢ የነበረው የመብት ጥሰቶች ቀንሰው እርዳታና የተሰደዱ ሰዎችን የመመለስ ሥራው ተጀምሯል፡፡ ቦታዎቹ ቀደም ብለው ሞትና ብጥብጥ ያስተናገዱ ነበሩ፡፡ በሶሪያ ያለው ስቃይ የተፈለገውን ያክል የዓለምን ቀልብ መሳብ አልቻለም፡፡ ባለፈው ዓመት በሽብርተኛው ቡድን አይ ኤስ ወደ አገራቸው የተመለሱ ንፁሃን መገደላቸው ይታወቃል፡፡ በዚህም በአገሪቱ በሚገኙ እርዳታ ፈላጊ ዜጎች እየተደረገ ያለው ድጋፍ የተገደበ እንዲሆን ማድረጉን ዘገባው አስታውሷል፡፡
አብዛኛው በስደት የሚገኙ ሶሪያውያን ከባለፈው የፈረንጆች ዓመት ጀምሮ ወደ አገራቸው እየገቡ ይገኛሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ብዙዎች እየተሰደዱ ይገኛሉ፡፡ ወደ አገራቸው ለሚመለሱ በየጊዜው የማስፈር ሥራ እየተሰራ ቢገኝም በቅርቡ ሦስት ጊዜ ነዋሪዎች ከአካባቢያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ የስደተኞቹ ቁጥር ከሚመለሱት ጋር ተመጣጣኝ እየሆነ መጥቷል፡፡ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ብቻ 66 ሺ ስደተኞች ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፤ ነገር ግን በአገሪቱ ባለው ጦርነት ከአካባቢያቸው የለቀቁ 300ሺ ዜጎች ወደ ጎረቤት አገራት ለማምለጥ ሲሞክሩ አልተሳካላቸውም፡፡ ወደ አገራቸው የተመለሱት ስደተኞች ሁኔታ ሲታይ አብዛኛው የተመለሱት በጉልበት እንደሆነ ማስረጃዎች እንዳሉ ዘገባው ያሳያል፡፡ ሌሎችም ወደ አገራቸው የሚመለሱት በስደተኝነት መኖር የሚያስችላቸው ሁኔታ ተስፋ ስላስቆረጣቸው መሆኑን ዘገባው ያትታል፡፡
አብዛኛው የሶሪያ ነዋሪ አገሪቱን ለቆ ከተሰደደ በኋላ አገሪቱ ወደ ፍርስራሽነት ተቀይራለች፡፡ አንድ ሦስተኛው በአገሪቱ የሚገኙ ቤቶችና ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ግማሹ የህክምና መስጫ ተቋማት በግጭቶች የመጎዳትና የመፍረስ አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡ እንደ ዓለም ባንክ ገለፃ የፈራረሱትን ወደነበረበት ለመመለስ ደግሞ ከ180 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያስፈልጋል፡፡ አገሪቱን ገንዘብ አውጥቶ ወደነበረችበት ከመመለሷ በፊት የተመሰቃቀለውን የፖለቲካ ሁኔታ ለማስተካከል በግጭት ላይ የሚገኙ ፓርቲዎችን ማስታረቅ በመቀጠል ደግሞ ድጋፍ የሚያደርጉ አገራት ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ለማድረግ ሁኔታዎች መመቻቸት እንዳለበት ዘገባው ይጠቁማል፡፡
የሶሪያን ስደተኞች ወደ አገራቸው መመለስ ሥራ በጥልቀትና በጥንቃቄ መከናወን አለበት፡፡ ለዚህም የእርዳታ ድርጅቶች ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በጦርነቱ ወቅት የተወለዱ ሕፃናት ሕጋዊ የሆነ ዜግነታቸውን የሚያሳውቅ ወረቀት የላቸውም። በዚህም ከፍተኛ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ነው ዘገባው የጠቀሰው፡፡ በተጨማሪም አብዛኛው ዜጋ በጦርነቱ ወቅት ትቶት የሄደው ቤቱና መሬቱን የሚያረጋግጥለት ወረቀት ስለሌለው ወደ አገሩ የሚመለስበት ምክንያት እንደሚያሳጣው ዘገባው ያሰያል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች የሚፈቱበት መንገድ ካልተፈጠረና ድጋፍ ካልተደረገ የነዋሪነት ማረጋገጫ የሌላቸውና የጠፋባቸው ሰዎች ወደ አገራቸው የመመለስ ጉዳይ አጠራጣሪ እንደሚያደርገው ዘገባው ያስረዳል፡፡
በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት በግጭት ውስጥ የሚገኙ ፓርቲዎች ለተሻለች ሶሪያ ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው፡፡ በተጨማሪም ፓርቲዎቹ ከስደት ወደ አገራቸው ለሚመለሱ ነዋሪዎች እኩል ትኩረት በመስጠት ስደተኞቹ አገራቸው ላይ እንዲቆዩና ሰላም እስኪመጣ እንዲጠብቁ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለጋሽ ድርጅቶችም ከጎረቤት አገራት ለሚመለሱ ስደተኞች በገቡት ቃል መሠረት ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ወደ አገራቸው ለሚመለሱ ስደተኞች ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ጎረቤት አገራት ባሳዩት ስደተኞች ያለመቀበል ፖሊሲ መሆን እንደሌለበት ዘገባው ያትታል፡፡
ዓለም አቀፍ ሕግ እንደሚለው ማንኛውም ስደተኛ በፈቃደኝነት ብቻ ወደ አገሩ መመለስ እንደሚችል ያስቀምጣል፡፡ የሰብዓዊ መብት ጠባቂ ተቋማትም በፈቃዳቸው የሚመለሱ ስደተኞች መርዳት፣ መስማትና መቆጣጠር አለባቸው፡፡ ለማንኛውም ስደተኛ በጉልበት ወይም ያለፈቃዱ ወደ አገሩ እንዳይመለስ ሁሉም አገር ድጋፍ ማድረግ አለበት፡፡
በአውሮፓና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የፖለቲካ ሰዎችና ዲፕሎማቶች ሶሪያን ለመጠበቅና ለመርዳት ቁጭ ብለው ማውራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ብዙ ውሳኔዎች በእጃቸው ላይ ይገኛል፤ ይህንን ዕድል መጠቀም ካልቻሉ ግን ችግሩ መልሶ የራሳቸው እንደሚሆን ዘገባው ያትታል፡፡
ቢቢሲ በድረገጹ እንዳሰፈረው ሶሪያ ወደ ለየለት ጦርነት በገባችባቸው ከ2013 አጋማሽ ጀምሮ ብቻ ከ250 ሺህ በላይ ሶሪያውያን ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን፣ ከ11 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ከሚኖሩበት ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡

መርድ ክፍሉ

Published in ዓለም አቀፍ

ያለንበት ዘመን የኢንፎርሜሽን ዘመን ነው፡፡ በዚህ የመረጃ ዘመን ደግሞ ለመረጃ ቅርብ መሆን ግድ ይላል፡፡ ምክንያቱም ከመረጃ በራቅን ቁጥር በርካታ ለሕይወታችን ወይም ለዕለት ተዕለት አኗኗራችን አጋዥ የሆኑ ቁምነገሮችን ልናጣ እንችላለን፡፡ ስለሆነም የመረጃ አጠቃቀማችን እንዴት ነው የሚለውንም ቆም ብሎ ማየት ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ትክክለኛና አስፈላጊ መረጃ የሚጠቅመንን ያህል የተዛባ መረጃ የሚያስከትለው ጉዳትም የዚያኑ ያህል ከባድ ነውና፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ መረጃ የሚሰራጭበትም ሆነ መረጃው ጥቅም ላይ የሚውልበት መንገድ የተዛባ ሆኖ እናገኛለን፡፡ በተለይ የማህበራዊ ሚዲያው መስፋፋትና ተደራሽነቱም እያደገ መሄድ ለዚህ ትልቁን ሚና እየተጫወተ እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡
በዛሬው ጽሑፌ የማህበራዊ ሚዲያው ላይ ትኩረት በማድረግ ጥቂት ነጥቦችን ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡ ለዚህ ያነሳሳኝ ዋናው ምክንያቴም በተለያዩ አጋጣሚዎች በፌስ ቡክ የተለቀቁ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ የተጋነኑና የተንሻፈፉ መረጃዎች ኅብረተሰቡ ጋር ሲደርሱና በእነዚህ መረጃዎችም አማካይነት በርካታ ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ሲጓዙ፣ አንዳንዶቹም እነዚህ በማህበራዊ ድረገፅ የሚሰራጩ መረጃዎች ሙሉ በሙሉ እውነት ናቸው ብለው አምነው መቀበላቸውና ሌሎችንም ለማሳመን ጥረት እስከማድረግ መድረሳቸው ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜ በእነዚህ ማህበራዊ ሚዲዎች የሚቀርቡ መረጃዎች በአሉባልታና በውሸት ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹም የውሸት ስያሜን ወይም አድራሻን እየያዙ በተሳሳተ ስም የተዛባ መረጃን የሚያሰራጩ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ በርካታ ግለሰቦችና ድርጅቶች በስማቸው የተከፈቱ የፌስ ቡክ አድራሻዎች እንደማይወክሏቸው ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ በርግጥም በዚህ ዓይነት የውሸት ስም የሚንቀሳቀሱ በርካታ የፌስቡክ ድረገፆች መኖራቸውንና እነዚህንም ለመቆጣጠር የሚያስችል ሶፍትዌር ተግባራዊ እንደሚደረግ የፌስቡክ መስራቹ ማርክ ሱከርበርግ በአንድ ወቅት ተናግሮ ነበር፡፡
በተለይ በታዋቂ ሰዎች ስም የሚፃፉና የሚሰራጩ አንዳንድ መረጃዎች ኃላፊነት የጎደላቸውና የሰዎችን ስምና ዝና እንዲሁም ሰብአዊ ክብርን እስከማዋረድ የሚዘልቁ ናቸው፡፡ ለአብነትም በሰላምና በፍቅር ከቤተሰቡ ጋር የሚኖርን አንድ ታዋቂ ሰው ስም በማንሳት “እከሌ ከትዳሩ ተፋታ”፣ “እከሌና እከሌ ተጣልተው ከባድ ችግር ተፈጠረ”፣”በዚህ አካባቢ ከባድ ጦርነት ተቀሰቀሰ”፣ “በዚህ አካባቢ በተከሰተ ግጭት የበርካታ ሰዎች ሕይወት አለፈ”፣ ወዘተ የሚሉ አሉባልታዎችን በፌስ ቡክ ወይም በተለያዩ ድረገፆች ላይ መመልከት የተለመደ ነገር ሆኗል፡፡
አንድ ገጠመኝ ላውጋችሁ፡፡ የዛሬ ሦስት ወራት ገደማ ነው፣ ጊዜው ጠዋት ሁለት ሰዓት አካባቢ ይሆናል፡፡ ከምኖርበት አካበቢ ተነስቼ ወደ መስሪያቤት በታክሲ እየሄድኩ ነው፡፡ በዚህ መካከል ሁለት ወጣቶች ባዩት ነገር በጣም ተደናግጠው እና ተረብሸው ሲጨዋወቱ ሰማሁ፡፡ ቀስ በቀስም የሚያወሩት ርዕሰ ጉዳይም ከጆሮዬ ገብቶ እኔንም ለድንጋጤ ዳረገኝ፡፡ ጉዳዩ አንድ ታዋቂ አርቲስት ሞቷል የሚል ዜና ነው፡፡ ይህ ሞቷል የተባለው አንጋፋ አርቲስት ደግሞ በወቅቱ ከአንድ ቀን በፊት በሚሌኒየም አዳራሽ ኮንሰርት ያቀረበ ሲሆን በዕለቱም እኔ በምሰራበት የሚዲያ ተቋም ከአንድ ጋዜጠኛ ጋር ቃለምልልስ ለማድረግ ቀጠሮ ነበረው፡፡ ከዚያ በፊት ስለ ጤና ጉድለቱ ምንም የተባለ ነገር አልነበረምና ዜናው አስደንጋጭ ነበር፡፡ በዚህ መካከል እኔም ክስተቱ እያሳዘነኝ መውረጃዬ ደርሶ ከታክሲ ወረድኩ፡፡ ወደ ቢሮም እንደገባሁ ከአርቲስቱ ጋር ቀጠሮ ከያዘው ጋዜጠኛ ጋር ተገናኘሁ፡፡ ስለመረጃውም ለማረጋገጥ የሰማሁትን ስነግረው እሱም ስለጉዳዩ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት መስማቱንና ነገር ግን እውነት መሆኑን አለማረጋገጡን ነገረኝ፡፡ ጥቂት ቦታዎች ከደዋወልን በኋላ በመጨረሻም ወሬው ውሸት መሆኑንና አርቲስቱም ምንም ዓይነት ችግር እንዳልገጠመው ማረጋገጥ ቻልን፡፡ እናም የተባለው ነገር አርቲስቱ ጋርም ደርሶ ስለነበር ጉዳዩ በጣም እንዳሳዘነው ነገረን፡፡ እኛም እንዲህ በሚያደርጉ ግለሰቦች ከማዘን ውጪ ምንም አማራጭ አልነበረንምና በጉዳዩ አዝነን አለፍን፡፡
በሌላ ጊዜም ተመሳሳይ ክስተቶች በፌስ ቡክ ወሬ በርካታ ሰዎች የሞራል ጉዳት እንደደረሰባቸው በተደጋጋሚ ሰምተን ይሆናል፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት የተሳሳቱ መረጃዎችን መስማት እንደወረርሽኝ ከተዛመተ ትንሽ ጊዜ ቆይቷልና፡፡ እንዲህ ዓይነት የሞራል ጉዳት ከደረሰባቸው ታዋቂ ሰዎች ውስጥም አርቲስቶች፣ ታዋቂ አትሌቶች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ነጋዴዎች፣ ተማሪዎችና ሌሎች የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይገኙበታል፡፡
ሰሞኑን በአንዳንድ የአገራችን ክፍሎች የተከሰቱ ግጭቶችን መነሻ በማድረግ በተለያዩ ድረገፆች የሚሰራጩ አንዳንድ መረጃዎች አሳዛኝም፣ አሳፋሪም ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ እነዚህ መረጃዎችም ሆን ተብለው ሕዝብን ከሕዝብ ለማበጣበጥና ለማጋጨት እንዲሁም ከፍ ሲልም አገሪቱን ለማፈራረስ ታስቦባቸው የሚፃፉ መሆናቸውን በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በተለይ ዘርን መሠረት በማድረግ የሚለቀቁት አንዳንድ መረጃዎች ምን ያህል አደገኛና በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥም ተሰምቶ የማይታወቅ እንዲሁም የሕዝቡን የርስ በርስ ቁርኝትና አብሮ የመኖር የቆየ እሴት ለመሸርሸር ታስቦ የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት በማይፈልጉ አካላት የሚሰራጭ መሆኑንም መገንዘብ ይቻላል፡፡
በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ሲከሰቱ የነበሩ አለመረጋጋቶች የተነሱበት ዋናው ምክንያት ኅብረተሰቡ በየጊዜው የሚያነሳቸው የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች በሚፈለገው ፍጥነት አለመሄዳቸው እንደሆነ መንግሥት በተደጋጋሚ ሲገልፀው የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመከታቸው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከግምገማ በኋላ ያለውን ችግር በዝርዝር አስቀምጠውታል፡፡ ያም ሆኖ ግን እነዚህን ሃሳቦች ወደ ጎን በመተው የፌስ ቡክ አጀንዳ ሆኖ የከረመው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተነሱ ግርግሮች በመንግሥት የተወሰዱ እርምጃዎች ከልክ ያለፉ ስለመሆናቸው፣ አንድን ብሔር ከሌላው ብሔር የሚያጋጩ፣ የእርስ በእርስ መተማመንን እሴት የሚያጠፉ፣ ሀገራዊ አንድነትን የሚሸረሽሩና መሰል ድርጊቶች ናቸው፡፡
በእርግጥ መንግሥት ለዜጎቹ ኃላፊነት እንዳለበት ማንም የማይክደው ሃቅ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በማንኛውም ጉዳይ ቅሬታ ላለውም ሆነ ለሌለው የኅብረተሰብ ክፍል እኩል ኃላፊነት እንዳለበት መረዳት አያዳግትም፡፡ ስለዚህ መንግሥት ሰላምን የማረጋገጥና ሰላማዊ ኑሮ እየኖሩ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን መንግሥት ለሚወስደው እርምጃ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡ ይህንን ጉዳይ ሚዛናዊ ሆኖ ማየት ተገቢ መሆኑን እያንዳንዱ ህሊናው የሚያመዛዝንና የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት አጥብቆ የሚመኝ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይረዳዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ከዚህ አንጻር በእነዚህ ድረገፆች ላይ በተደጋጋሚ የሚለቀቁት መረጃዎች ምንም ዓይነት ጥፋት ሳይሰራ ችግር የደረሰበትን የኅብረተሰብ ክፍል ከመወገን ይልቅ በሕገወጥ መንገድ የሌላውን ንብረት ለሚያወድሙት የሚያደላ ነው፡፡ ለመሆኑ በአገሩ ላይ በሰላማዊ መንገድ ሰርቶ የመኖር መብት የሁሉም ዜጋ አይደለምን? በትክክልም እያንዳንዱ ዜጋ በአገሩ ላይ ሰርቶ የመኖር መብት አለው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም እያንዳንዱ ዜጋ በአገሩ በሰላም ወጥቶ በሰላም የመግባት መብትም አለው፡፡ ነገር ግን ይህ እንዳይሆን የተለያየ ምክንያት በመፍጠር በሀገሪቱ ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር የሚጥሩ አካላት አሉ፡፡ በዚህ ብቻም ሳያበቁ ጥቂት ግርግር ሲነሳ ዜጎች ለዘመናት ለፍተው ያጠራቀሙትን ሀብትና ንብረት እንዲሁም የሁላችንም የጋራ ሀብት የሆኑትን የመንግሥት ንብረቶች የማውደም ዓላማን ይዘው የሚንቀሳቀሱም አሉ፡፡ እነዚህን ኃይሎች በፌስ ቡክ ሃይ የሚል ግን ብዙም አይታይም፡፡ ቢኖርም አደርባይ በሚል ይፈረጃል፡፡
ከሁሉም በላይ የሚገርመው ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ በእነዚህ የፌስቡክና ሌሎች ማህበራዊ ድረገፆች በመጠቀም ብጥብጥ እንዲፈጠር የሚያደርጉ አካላት ለራሳቸው የተመቻቸ ቦታ እና ምቹ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ሌሎችን ለዚህ ነውጥና ሁከት የሚጋብዙበት ሁኔታ በስፋት መኖሩ ነው፡፡ ለምሳሌ መኖሪያውን ውጭ አገር ያደረገው ጁሃር መሃመድ አንድ ሰሞን እዚያ ተቀምጦ እዚህ የጦር ጄኔራል ሲሆን ተመልክተናል፡፡
ከዚያም አልፎ ለራሱ ምንም ዓይነት አደጋና ችግር እንደማያጋጥመው ጥግ ይዞ ሌሎችን ተነስ ወደ ከመንግሥት ጋር ተዋጋ፣ ያለህበት ኑሮ ምቹ አይደለም፣ ሌሎች አካላት ከሚገዙህ እኔ ብገዛህ ይሻላል በሚል ስሜት ሌሎችን መገፋፋት እና ለጦርነት ማነሳሳት የቻለው በዚሁ በፌስ ቡክ ዘመቻ ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ አንዳንድ ሰዎች የፌስ ቡክ መረጃዎችን የዕለት ተዕለት የመረጃ ምንጭ በማድረግ እከሌ እንዲህ አለ፤ እከሌ እንዲህ አደረገ በማለት ያልተረጋገጡ መረጃዎችን ከራሳቸው አልፈው ወደ ሌሎችም ሲያሰራጩ መዋላቸው ነው፡፡
የሶሻል ሚዲያው ያስከተላቸው በርካታ ችግሮች ውስጥ አንዱ ደግሞ የባህል ወረራ ነው፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት በእነዚህ ሚዲያዎች በነፃነት የሚሰራጩ አንዳንድ መረጃዎችና ቪዲዮዎች በተለይ ወጣቱን ለከፍተኛ የሥነምግባር ብልሽት የሚዳርጉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በእነዚህ ሚዲያዎች አማካይነት ልቅ የወሲብ ፊልሞች፣ ከባህል ውጪ የሆኑ ድርጊቶችና ሌሎች የሥነምግባር ችግር የሚያስከትሉ መረጃዎች ይተላለፋሉ፡፡ እነዚህ ደግሞ ልቅ ለሆነ የወሲባዊ ግንኙነትና በዚህም ሳቢያ ለኤች አይቪ/ኤድስና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች መስፋፋት ዋነኛ ምክንያት የሚሆኑበት ሁኔታም ሰፊ ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በአሁኑ ወቅት እነዚህ ማህበራዊ ሚዲዎች በቀላሉ በምንይዛቸው ሞባይል ስልኮቻችን አማካይነት ሊተላለፉና ሊሰራጩ የሚችሉ መሆናቸው የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በቀላሉ እንዲያገኟቸው በር ከፍቷል፡፡ በተለይ ገና በለጋ ዕድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶችና ሕፃናት ጭምር በቀላሉ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን የሚያገኙበት ዕድል እየሰፋ በመጣበት በአሁኑ ወቅት እነዚህን የፌስ ቡክ መረጃዎች የሚያገኙበት ዕድልም በዚያው ልክ እየሰፋ መጥቷል፡፡
ከሁሉም በላይ በአሁኑ ወቅት ማህበራዊ ሚዲያውን እየከፋ እንዲሄድ ካደረጉ ችግሮች ውስጥ አንዱ ደግሞ የዘረኝነት ማስፋፊያ እየሆነ መምጣቱ ነው፡፡ በተለይ ዘርን መሠረት በማድረግ የአንዱ ብሔር በሌላው ብሔር ላይ ጥላቻ እንዲያሳድር ለማድረግ የተለያዩ ያልተፈጸሙ እና ሆን ተብለው የሚቀነባበሩ ሃሳቦችን በመለጠፍ እርስ በርስ ለማጋጨት የሚደረጉ ጥረቶች ማህበራዊ ሚዲያው ኃላፊነት የጎደለው ሚዲያ መሆኑን እንድንገነዘብ የሚያደርግ ነው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ የተለያዩ ከ80 በላይ ቋንቋዎች የሚነገሩባትና የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች አገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ እንዲህ ባለችው አገር ዘርን መሠረት ያደረገ የጥላቻ ፖለቲካን የሚያራምዱ አካላት ፍላጎታቸው ማቆሚያ የሌለው የእርስ በርስ ግጭትና እልቂት ለመጋበዝ ካልሆነ በስተቀር ምን ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ ያውም በተቀነባበረ ውሸት አማካይነት ሆን ብሎ ሰዎችን እርስ በርስ ለማጋጨት መሞከር ጤነኛ አስተሳሰብ ካለው ዜጋ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ እናም ይህንን እኩይ ድርጊት የሚያራምዱ አካላት ኃላፊነት የጎደላቸውና በማህበራዊ ሚዲያ ተደብቀው ድብቅ አላማቸውን የሚያራምዱ አካላት መሆናቸውን መረዳት ተገቢ ነው፡፡
በርግጥ የሶሻል ሚዲያው ተጽዕኖ በአገራችን ብቻም ሳይሆን በተለያዩ የዓለም ክፍሎችም የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ ያለ መሣሪያ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለአብነትም ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የተጀመረውና የተለያዩ የአረብ አገራትን ያዳረሰው ግጭት ሊባባስ የቻለው በፌስ ቡክ አማካይነት ነው፡፡ በግብፅ በተደጋጋሚ ታህሪር አደባባይ ይወጡ የነበሩ ሰልፈኞች ፌስቡክን ዋነኛ የመገናኛ መስመር አድርገው ተጠቅመውበታል፡፡
እነዚህ ሶሻል ሚዲያዎች በራሳቸው የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤቶች በመሆናቸው በአግባቡ ብንጠቀምባቸው ጠቀሜታቸው እንደሚጎላ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን እነዚህን መሣሪያዎች ያለአግባብ መጠቀም ደግሞ የራሱ አሉታዊ ተጽዕኖ አለው፡፡ በተለይ በእነዚህ ሚዲያዎች የሚተላለፈው መረጃ ባለቤት የሌለው በመሆኑ ሁሉም ሰው እንደልቡ የሚያሰራጨው መረጃ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ የሚተላለፉት መረጃዎች በግዴለሽነት የሚጻፉ፣ የተሳሳቱና ሆን ተብለው ሰዎችን ለማሳሳት የሚቀርቡ ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል ከፍተኛ ነው፡፡
ስለዚህ ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ ካልተረዳነውና የመረጃ ምንጩን ከሌሎች የሚዲያ አካላት ሳናረጋግጥ እንደወረደ የምንወስደውና ያንኑ መልሰን ለሌሎች አካላት የምናስፋፋ ከሆነ እኛ ተሳስተን ሌሎችንም እንዳናሳስት ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል፡፡ ሞተ ሲሉት ተሰበረ የሚል አንዳንዴም ከዚያም በላይ የራስ ፍላጎትን በፌስ ቡክ አማካይነት ለማራመድ መረጃዎችን የሚፈበርክ በርካታ ኃይል ባለበት ነባራዊ ሁኔታ እነዚህን መረጃዎች በጥንቃቄ መመልከትና መረዳት ተገቢ ነው፡፡ በተለይ በእነዚህ መረጃዎች እየተመራን ባልተገቡ ድርጊቶች ውስጥ የምንሳተፍ ካለንም ቆም ብለን ማሰብ ይጠበቅብናል፡፡ ካልሆነ ግን የሚያስከትለው አደጋ የከፋ ይሆናልና፡፡

ወርቁ ማሩ

Published in አጀንዳ

ሀገራችን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለም ላይ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ ሀገራት በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች፡፡ በተለይ ባለፉት አስር ዓመታት እያስመዘገበች ያለው ተከታታይ ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት በሀገሪቱ ለዘመናት ስር ሰዶ የኖረውን የድህነትና የኋላቀርነት ታሪክ በመሻር መካከለኛ እድገት ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ የሚያስችል እንደሆነ ይታመናል፡፡ ያም ሆኖ ግን የታለመውን ግብ ለማሳካት የተጀመረውን የልማትና የእድገት ጉዞ ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል ብቻ ሳይሆን ቀደም ሲል ከነበረው ፍጥነት ይበልጥ ትግል ማድረግን ይጠይቃል፡፡ መንግሥትም ይህንን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በርካታ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
በዚህም መሠረት በሀገሪቱ መሠረታዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ለማምጣት የሚያስችል የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ተግባራዊ በማድረግ ባለፉት ስምንት ዓመታት አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል፡፡ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ትግበራም የታዩትን በጎ ጅምሮች ለማስቀጠልና በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድም የተሻለ ለውጥ ለማምጣት ዘርፈብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በአንጻሩ ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እነዚህ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ለውጦች በሚፈለገው ስፋትና ግለት እንዳይጓዙ የሚፈታተኑ ችግሮች እየታዩ መጥተዋል፡፡ በዚህ የተነሳም የሕዝቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማስፋት፣ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ የግልፅነትና የተጠያቂነት አሠራርን ለማንገስና ውጤታማና ቀልጣፋ አስተዳደር ለመገንባት የተደረጉ ጥረቶች ያስገኙትን መልካም ፍሬ መጠበቅና ማስፋት አዳጋች ሆኖ መቆየቱን መንግሥት በየደረጃው ባደረገው ግምገማ አረጋገጧል፡፡
በዚህ የተነሳ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ኅብረተሰቡ ቅሬታዎችን ሲያሰማ መስማት የተለመደ ተግባር እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህ በአንድ በኩል ኅብረተሰቡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ፍላጎቱ እያደገ መምጣቱንና ለዚህ ፍላጎቱም የሚገባውን ለማግኘት መንግሥትን መጠየቅ በመጀመሩ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይህ ደግሞ መንግሥት የልማት እና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይ የጀመራቸውን ጥረቶች ይበልጥ በማጠናከር በፍጥነት መጓዝ እንዳለበት የሚያመላክት ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የሚነሱት ቅሬታዎች በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት በቅን ልቦናና መንግሥታዊ መመሪያዎችን በተከተለ አኳኋን ሕዝቡን የሚያገለግሉበትና ተሳትፎና ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጡበት እድል እየቀነሰ መሄድና የቁርጠኝነት ማነስ የችግሩ ዋነኛ መንስኤዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በሙስናም ሆነ በሌሎች ጥፋቶች ውስጥ የተዘፈቁ ግለሰቦችን በወቅቱና ሕጋዊና አስተማሪ በሆነ መንገድ መጠየቅ አለመቻል፣ መንግሥት የሕዝብና የአገር ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በነደፋቸው ፕሮጀክቶች ዙሪያ የሚታዩ የአፈፅፀምና የሥነምግባር ችግሮችን አስተማማኝና ውጤታማ በሆነ መንገድ የማረምና የማስተካከል ጉድለት፣ በሁሉም መስክ ተወዳዳሪ ሊያደርጉና የሕዝባችንን ተጠቃሚነት ሊያሰፉ የሚችሉ ፕሮጀክቶች፣ የጊዜ መጓተት፣ የዋጋ ንረትና የሀብት ብክነት የሚታይባቸው መሆን እንዲሁም በየዘርፉ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በተግባር ማቃለል ሲገባ ባጉል ተስፋና በባዶ ቃልኪዳን የመሸንገል ሕዝበኛ አዝማሚያዎች መታየታቸው ዋነኛ የሕዝብ ቅሬታ ምንጮች እንደነበሩ በተደረጉ ግምገማዎች ማየት ተችሏል፡፡
ስለዚህ እነዚህን ችግሮች መፍታት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ ባለመሆኑ መንግሥት ከከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ግምገማ ማግስት ጀምሮ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግና መስተካከል ያለባቸውን ችግሮች ለማረም ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ በየደረጃው ያለው የመንግሥት አስፈጻሚ አካል ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የአገልጋይነት መንፈስ ተላብሶ የሕዝቡን ጥያቄዎች በአፋጣኝ ለመመለስ እንዲችል የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም በተለይ ቀደም ሲል በተፈጠሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ውስጥ በተጨባጭ ችግሮችን የፈጠሩ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞችም ተጠያቂ እንዲሆኑ እየተደረገ ይገኛል፡፡
ሀገራችንን አሁን ካለችበት ወቅታዊ ችግር ለማውጣትና የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል ኅብረተሰቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት ወቅቱ የሚፈልገው መሠረታዊ ምላሽ ነው፡፡
ስለዚህ በቀጣይ ሕዝቡ ያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስና የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ለውጦችን ማስቀጠል በየደረጃው ካለው የመንግሥት መዋቅርና ሠራተኛ እንዲሁም ከመላው ኅብረተሰቡ የሚጠበቅ በመሆኑ ሁሉም በተሰማራበት የሥራ መስክ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣትና ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

አዲስ አበባ፡- በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርታቸውን እስከ አስረኛ ክፍል መቀጠል ያልቻሉና በመደበኛ የሙያ ፕሮግራም ገብተው መማር ያልቻሉ ወጣቶችን በተለያዩ ሙያዎች በማሰልጠን ለስደት ተጋላጭነትን መቀነስ እንደሚቻል ተገለፀ፡፡

የሰላም ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ከዶርቃስ ኤድ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በተለያዩ ሙያዎች ያሰለጠናቸውን 287 ወጣቶች ከትናንት በስትያ አስመርቋል፡፡ የሰላም ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ዲን አቶ ሰለሞን ሜሊ እንዳሉት፤ በየካ ክፍለ ከተማ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች የተወጣጡ ስራ አጥና ለስደት ተጋላጭ የሆኑ ወጣቶችን በመጀመሪያ ዙር 208 ወጣቶች በዘጠኝ የሙያ መስክ ስልጠና ወስደዋል፡፡ የተሰጠው ስልጠናም ወጣቶች ለስደት ተጋላጭ እንዳይሆኑ እገዛ ያደርጋል፡፡
ሰልጣኞቹ ለስድስት ወራት ስልጠና የወሰዱ ሲሆን ከዚህም ውስጥ ሁለት ወራት በኢንዱስትሪዎች ውስጥ የተግባር ትምህርት መውሰዳቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ሰልጣኞቹ የስራ እድል የተፈጠረ ሲሆን 110ሩ በቅጥር ስራ አግኝተዋል፤ 87 ሰልጣኞች ደግሞ በጥቃቅንና አነስተኛ እንዲደራጁ ወደየመጡበት ወረዳ ሲላኩ የተቀሩት ስራ እየተፈለገላቸው እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
የዶርቃስ ኤድ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ፍቅሩ ታረቀኝ በበኩላቸው፤ ከሰላም ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ጋር በመተባበር 208 ወጣቶች ከሰላምና 79 ከዶርቃስ ማሰልጠኛ ስልጠና የወሰዱ ወጣቶች መመረቃቸውን ጠቁመዋል፡፡ ወጣቱ ትምህርቱን አቋርጦ ወደ ስደት እንዳይሄድ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ዶርቃስ በእንጨት፣ በብረታብረትና በልብስ ቅድ ስልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትር ደኤታ ተወካይ አቶ ብዙነህ አዱኛ፤ ወጣቱ ስራ አጥና ለስደት ተጋላጭ እንዳይሆን እየተሰጠ ያለው ስልጠና መቀጠል እንዳለበት ጠቅሰው፤ ስልጠና የወሰዱ ወጣቶች ተመልሰው ስደት እንዳያስቡ የፋይናንስ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

መርድ ክፍሉ

Published in የሀገር ውስጥ

አዲስ አበባ፡- በክልሉ በድርቅ የተጎዱትን መልሶ ለማቋቋም የተከናወኑትን ዘርፈ ብዙ ተግባራት ቀጣይነት ለማረጋገጥ ተግቶ እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ፡፡

በክልሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የከተሞች መልካም አስተዳደርና አቅም ግንባታ ዋና የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ሰመተር ፈለግ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ አርብቶ አደርነትን መተዳደሪያው ያደረገው ህብረተሰብ በድርቁ ሳቢያ ከብቶቹን አጥቷል፡፡ መንግስትም ይህንን በመገንዘብ ቅድሚያ አንገብጋቢው የመኖሪያ ቤት በመሆኑ በክልሉ የገጠር ቤት ኪነ ህንፃ ተዘጋጅቷል፡፡ አንድ ማሳያ ቤት ተሰርቶም በዛ መሰረት በሁሉም ወረዳዎች እንዲሰራ ተደርጓል፡፡ በዚህም ከ3 ሺህ 30 ቤቶች በላይ በ93 ወረዳዎች በተለዩ የከተማ ገጠር ቀበሌዎችና በወረዳ ገጠር ቀበሌዎች በማዘጋጀት ተጎጂዎችን የማስፈር ስራ ተሰርቷል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም ለፍየል፣ ለበግ፣ ለዶሮ፣ ለንብ ማነብ እንዲሁም ለከብቶች እርባታ አገልግሎት የሚውሉ 558 የከብት እርባታ ሼዶች ተገንብተዋል፡፡
እንደ አቶ ሰመተር ገለፃ፤ ለነዋሪዎቹ መኖሪያ ቤት ከመስራት ባሻገር ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ተደርጎ የተወሰደው ከአርብቶ አደርነት እንዲወጡ ማድረግ ሲሆን ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከ1 ሺህ 40 ሔክታር በላይ የእርሻ መሬቶች ተሰጥቷቸዋል፡፡ በክልሉ መሬት በስፋት ያለ ቢሆንም የውሃ ችግር አሳሳቢ በመሆኑ ለእርሻ ስራውና ለተገነቡት የእርባታ ሼዶች የሚሆኑ 41 የውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮም ተከናውኗል፡፡ ውሃ በማይገኝባቸው አካባቢዎችም ማቆሪያ ተዘጋጅቷል፡፡ ስራው ቀጣይነት እንዲኖረው ለማስቻልም በየወረዳው እስከ ሶስት የሚደርሱ የውሃ ግድብ እንዲሰራ ተደርጓል፡፡
ቀድሞ ህይወቱን በአርብቶ አደርነት ይመራ የነበረው የህብረተሰብ ክፍልም ወደ እርሻ እንዲገባ በእያንዳንዱ ወረዳ ሞዴል እርሻዎችን በማዘጋጀት ሰርቶ ማሳያ ስራ ተካሂዷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ህብረተሰቡ በተደረገለት የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ በመነሳት ለውዝ፣ በቆሎ፣ ማሽላ እና መሰል ምርቶችን እያመረተ ይገኛል፡፡ በዚህም በዘላቂነት በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ተችሏል፡፡ በቀጣይም ትልቁ የትኩረት አቅጣጫ በወረዳዎችና በከተሞች ላይ በአርብቶ አደርነት ይተዳደር የነበረው የህብረተሰብ ክፍል እርሻ ላይ እያከናወነ ያለውን ተግባር ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ምርትና ምርታማነቱን ማሳደግና ከአካባቢው አልፎ ገበያ ተኮር ስራዎችን እንዲሰራ ማስቻል ይሆናል ብለዋል፡፡

 

ፍዮሪ ተወልደ

Published in የሀገር ውስጥ

ወይዘሮ ዘምዘም ሲራጅ ይባላሉ። በአፋር ክልል አሚባራ ወረዳ የባዳሀሙ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ከዚህ ቀደም በክልሉ በስፋት በሚታወቀው የጥጥ ምርት እና የእንስሳት እርባታ ላይ በመሰማራት ኑሯቸውን ይመሩ ነበር። ከ2006 ዓ.ም በኋላ ግን በተጨማሪ በመሬታቸው ላይ የዳቦ ስንዴ ሰብልን በመስኖ ማምረት የሚያስችል እድል አገኙ። ይህን አጋጣሚ የፈጠረላቸው የፌዴራል የግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት ስር የሚገኘው የወረር የግብርና ምርምር ማዕከል ነው። በዚህም በአካባቢው ይሆናል ተብሎ የማይታሰበውን እህል ማምረት ችለዋል።

የስንዴ ምርት እነ ወይዘሮ ዘምዘም በሚኖሩበት ክልል መብቀል ይችላል ተብሎ አይታሰብም ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ቆላማና እርጥበት አጠር አካባቢ ነው። ሆኖም የግብርና ምርምር ማዕከል ይህን ሁሉ ተቋቁሞ ፍሬ ማፍራት የሚችል የስንዴ ሰብልን በተመረጡ የአርብቶ አደሮች እና ከፊል አርብቶ አደሮች መሬት ላይ በማሳያነት በመስኖ በመዝራት ውጤት በማምጣቱ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
የግብርና ምርምር ማዕከሉ ለወይዘሮ ዘምዘም እና በአካባቢው ነዋሪ ለሆኑ አርብቶ አደሮች ቆላማነትን ተቋቁሞ መብቀል የሚችል እና በምርቱም ውጤታማ የሆነ እንዲሁም በመስኖ የሚለማ ስንዴን በምርምር ለይቶ ከመስጠት ጀምሮ የቴክኖሎጂ ድጋፍ እና የሙያ እገዛ እያደረገላቸው ይገኛል። በዚህም ወይዘሮ ዘምዘምም በስድስት ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በማምረት ላይ ናቸው።
«ከዚህ ቀደም የጥጥ ምርት ላይ ትኩረት በማድረጋችን በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነበር የምናመርተው» የሚሉት አርሶአደር ዘምዘም፤ የግብርና ምርምር ማዕከሉ ያስተዋወቃቸውን የስንዴ ምርት በመስኖ በማልማታቸው በዓመት ሁለት ጊዜ መሬቱን መጠቀም እንደቻሉ ይናገራሉ። ሆኖም የአካባቢው ማህበረሰብ ሙሉ ለሙሉ በዚህ ስራ ላይ አልተሰማራም። ሰፊ የአመለካከት ስራ መስራት እና ሰብል ማምረት እንዲችል የሚመለከተው አካል ግንዛቤ ማስጨበጥ እንዳለበት ያስረዳሉ።
በተመሳሳይ በ40 ሄክታር መሬት ላይ ከጥጥ በተጓዳኝ የመስኖ ስንዴን በማምረት ላይ የሚገኙት አቶ ሀጂ አህመድ በበኩላቸው፤ በክልሉ የማይቻል የሚመስለው የሰብል ምርት በተግባር በምርምር ማዕከሉ አማካኝነት ተረጋግጧል። ምርቱም ውጤታማ እንደሆነ አረጋግጠናል ይላሉ። የአካባቢው ማህበረሰብም በዚህ ስራ ላይ በቁርጠኝነት መሰማራት ይኖርበታል የሚል ጥሪያቸውን ያስተላልፋሉ።
አቶ ደስታ ገብሬ የወረር የግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር እና የመስኖ ስንዴ ተመራማሪ ናቸው። ቆላማና እርጥበት አጠር በሆነው የአፋር ክልል መጠነኛ ቅዝቃዜ በሚፈጠርበት ወቅት ላይ በመስኖ ስንዴን ማምረት እንደሚቻል ይናገራሉ። በዚህም ማዕከሉ ሰባት የስንዴ ዝርያዎችን በምርመር በመለየት በአካባቢው ሞክሮ በስፋት ምርት እንደሚሰጡ ተረጋግጧል። ከነዚህ ውስጥ አንዱ የመኮሮኒ ስንዴ እንደሆነም ጠቁመዋል።
የምርምር ማዕከሉ ዳይሬክተር እንደሚናገሩት፤ ስንዴን የአርብቶአደር እና ከፊል አርብቶአደር በስፋት በሚኖርበት የአፋር ክልል ማምረት ከተቻለ የማህበረሰቡን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጡም በላይ ለሌሎች አካባቢዎች የሚተርፍ ከሰፋፊ የመስኖ እርሻ መሬት ላይ አግኝቶ ማሰራጨት ይቻላል። ነገር ግን የተገኘውን ውጤት ለማስፋት የቅንጅት ስራ ያስፈልጋል።
የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ለአካባቢው ተስማሚ የሆኑ ምርጥ ዝርያዎችን ለይቶ ማቅረቡ እና በተወሰኑ አካባቢዎች እንዲስፋፉ ማድረጉ ብቻ ፋይዳ የለውም የሚል እምነት እንዳላቸው የሚገልጹት ተመራማሪው አቶ ደስታ፤ የክልሉ እና የፌዴራል የግብርና መስሪያ ቤቶች የማህበረሰቡን ግንዛቤ ከማስፋት ባሻገር የቴክኖሎጂ ድጋፍ በማድረግ፣ የመሬት ሽፋንን እና የተሳታፊ ቁጥርን በማሳደግ ስራ መስራት እንዳለባቸው ያስገነዝባሉ።
አቶ አደም ሀሸን በአፋር ክልል የአሚባራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ናቸው። የወረር የግብርና ምርምር ማዕከል በአካባቢው ሊበቅሉ እና ከፍተኛ ውጤት ሊሰጡ የሚችሉ የመስኖ ስንዴ ዝርያዎችን በአካባቢው አርብቶአደር እና ልማታዊ ባለሀብቶች ማሳ ላይ በመዝራት ውጤት ማግኘት መቻሉን አሳይቶናል ይላሉ። በክልሉ ሰብልን በመስኖ ማምረት የማይቻል ተደርጎ ሲወሰድ ቆይቷል። ይሁን እንጂ አሁን ይሄን አመለካከት ስህተት የሚያደርግ የምርምር ውጤት አግኝተናል። ይህ ደግሞ የማህበረሰቡን አመለካከት በመቀየር እንዲሁም ልማታዊ ባለሀብቱ የአዋሽ ወንዝን ተጠቅሞ በሰፋፊ እርሻዎች ላይ ስንዴን እንዲያመርት እንደሚያግዘው ያስረዳሉ። በዚህም የወረዳው አስተዳደር የግብአት አቅርቦት እና ምቹ የገበያ ትስስርን በመፍጠር ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚሰራ ይናገራሉ።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ለቆላማው የአገራችን ክፍሎች ተስማሚ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን የማላመድ፣ የማፍለቅ እንዲሁም የማስተዋወቅ ስራን ይሰራል። በዚህም በሰብል ምርት ዘርፍ የጥጥ፣ ሰሊጥ፣ ለውዝ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ፣ ስንዴ፣ ሩዝ እና ሌሎች ምርቶች ላይ ይመራመራል። በአፈርና ውሃ ምርምር ዘርፍ በአፈር ቅኝት፣ በአፈር ጨዋማነት፣ በመስኖ ውሃ እንዲሁም በሌሎች መሰል የምርምር ዘርፎች ላይ ይሰራል።

ዜና ሀተታ
ዳግም ከበደ

Published in የሀገር ውስጥ

አዲስ አበባ፡- በጋምቤላ ክልል ለወጣቶች የተመደበውን የተዘዋዋሪ ፈንድ ብድር ለማግኘት የቤት ካርታ መጠየቁ በበርካታ ነዋሪዎች ዘንድ ቅሬታን መፍጠሩን የፌዴራል የስራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ገለፀ፡፡

በኤጀንሲው ተጠባባቂ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሙሉዓለም ስሜ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ በክልሉ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ተጠቃሚ ለመሆን ከመመሪያ ውጪ የቤት ካርታ እንደሚጠየቅ ኤጀንሲው ለድጋፍ በወረደበት ወቅት ማረጋገጥ ችሏል፡፡
በዚህ የተነሳም የክልሉ ስራ አጥ ወጣቶች ‹‹የቤት ካርታ የሌለን በመሆኑና፣ ካርታ ማስያዝ ባለመቻላችን የእድሉ ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም›› የሚል ጥያቄን ያነሳሉ ብለዋል፡፡ ይህ ደግሞ በክልሉ የመልካም አስተዳደር ችግር መነሻ እንደሚሆን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል የስራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ቢሮ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ኡጁሉ ጊሎ እንደሚያስረዱት፤ ተዘዋዋሪ ፈንድ ላይ ይህን አማራጭ እንደመፍትሄ ተደርጎ የተወሰደው ወጣቶች ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ከግል ፍላጎት በመነጨ የተደረገ ሳይሆን ከዚህ ቀደም ያጋጠሙንን ችግሮች መነሻ በማድረግ ነው ብለዋል፡፡
አቶ ኡጁሉ እንደገለፁት ከዚህ ቀደም ክልሉ ለወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ 10 ሚሊየን ብር በጅቶ ከዚህ ውስጥ አራት ሚሊየኑ ለአነስተኛ ብድር ተቋም ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም ግማሽ ሚሊየን እንኳ ተመላሽ አልተደረገም ብለዋል፡፡ በመሆኑም ብድር ሲወሰድ ተመላሽ መደረግና ሌሎች ስራ ፈላጊዎች ደግሞ በዚህ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ለማስገንዘብ ታስቦ የቤት ካርታ ተጠይቋል፡፡
ያም ሆኖ ግን በክልሉ በርካታ ወጣቶች ስራ አጥ መሆናቸው ከክልሉ አልፎ ለአገርም ስጋት መሆኑንና ካርታ መጠየቁም ማነቆ መሆኑን ምክትል ዳይሬክተሩ አልሸሸጉም፡፡ ከተለዩት 11 ሺህ ስራ አጦች ሁለት ሺህ የሚሆኑት ብቻ የተዘዋዋሪ ፈንድ ብድር አገልግሎት አግኝተው ወደ ስራ ገብተዋል፡፡ ይህም የሆነው በክልሉ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ያላቸው እንዲሁም የሌላቸው ደግሞ የይዞታ ማረጋገጫ ካርኒ በማቅረብ ነው፡፡ አገልግሎት አሰጣጡም ችግር በመሆኑና ካርታ ማስያዝም ዘላቂ መፍትሄ ባለመሆኑ ህዝቡን በተዘዋዋሪ ፈንድ በታሰበው ደረጃ ተጠቃሚ ለማድረግና ጎን ለጎንም ተመላሽ ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
በተመሳሳይ በክልል ደረጃ ብድር ወስደው ተመላሽ የማያደርጉ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ ላይ በአሰራር የሚታዩ ጉድለቶች አሉ፡፡ይህንንም ጉዳይ ከሌሎች ክልሎች ተሞክሮ በመውሰድ ለማሻሻል ይሰራል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የፌደራል የስራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ተጠባባቂ ዳይሬክተሩ አቶ ሙሉዓለም ስሜ እንደሚሉት ክልሉ ካርታ ለመጠየቅ እንደ አንድ ምክንያት ያቀረበው አካባቢው ድንበር ላይ በመሆኑ መንግስት የሚያመቻቸውን ብድሮች ይዞ የመጥፋት ችግሮች በስፋት በመኖሩ ነው ማለቱን ጠቅሰው ይህ ግን ትክክል አይደለም ብለዋል፡፡
ችግሩ የተፈጠረው በክልሉ የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ በቂ ግንዛቤ ባለመፈጠሩ እንደሆነ ጠቁመው ይህም በብድር አመላለሱ ላይ አሉታዊ አስተዋፅዖ አበርክቷል ብለዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በጀቱ የሚፀድቀው በክልሉ መሆኑና አሳታፊነት ላይ ችግር መኖሩ ተግዳሮት ነው፡፡
ችግሩን ለመፍታት በብድር አሰጣጥና አመላለስ ዙሪያ ኤጀንሲው ምን መደረግና እንዴት መሰጠት እንዳለበት የክልሉ አመራሮች ባሉበት ከዘርፍ ምክር ቤት አባላት ጋር ውይይት የተደረገበት መሆኑንና አሰራሩም ከመመሪያ ውጪ የተከናወነ በመሆኑ እንዲስተካከል አቅጣጫ ተቀምጦበታል ብለዋል፡፡

ፍዮሪ ተወልደ

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።