Items filtered by date: Tuesday, 13 February 2018

በኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ በፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና ሪፖርት ኦዲት ቁጥር 847/2006 አንቀፅ አራት አንድ ላይ እንደተመለከተው ቦርዱ በሚኒስተሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 332/2007 የተቋቋመ መንግስታዊ መስሪያ ቤት ነው። ተቋሙ መንግስት በአገሪቱ የግልና የመንግስት ድርጅቶች ላይ ተፈፃሚ እንዲሆን ያወጣው የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ አዋጅን መሰረት በማድረግ ነው የተቋቋመው።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከቦርዱ ዋና ዳይሬክተር አማካሪና የፅህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ደመላሽ ደበሌ ጋር የፋይናንስ ሪፖርት አቀራርብ ስርዓትን በአግባቡ መከወን ስላለው ፋይዳ፤ አጠቃላይ ስለ ቦርዱ ተግባራትና እያጋጠሙ ስላሉ ተግዳሮቶች ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ከአዋጁ በፊት የአገሪቱ ፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ የነበረው ገፅታ
ይህ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት በመንግስትም ይሁን በግሉ ዘርፉ ያሉ ድርጅቶች ሊከተሉት የሚገባ ዝቅተኛ ወይንም ተቀባይነት ያለው ወጥ እና ማንኛውም ሰው በቀላሉ የሚረዳው የሪፖርት አቀራረብ ስርዓት አልነበረም። አንድ ወጥ የሆነና የአገሪቱን እድገት ታሳቢ ያደረገ ወቅቱ በሚጠይቀው ደረጃ ዘመናዊ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ስርዓትን የሚመራ ህግም አልነበረም። ያሉትም ህጎች ቢሆኑ ድርጅቶች በተመቻቸው መንገድ የሚያወጧቸው ናቸው።
አቶ ደመላሽ ለአብነትም ታክስን በመውሰድ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ስለሚጠይቀው ሪፖርት ያብራራሉ። ሪፖርቱ ወጥ በሆነ እና ተቀባይነት ባለው መልኩ ተሰርቶ የሚቀርብ ባለመሆኑ መንግስት ሊሰበስብ የሚገባው ግብር በአግባቡ እንዳይሰበስብ አድርጎታል። ግብሩ አንዱ ላይ ከፍተኛ ሌላው ዘንድ ዝቅተኛ የሚሆነውም በዚህ ምክንያት ነው ይላሉ።
ከዚህ በተጓዳኝ ቁጥሮች ትመለከታለህ፤ ከቁጥሮቹ ጀርባ ያለውን አታውቅም። ይህን ያህል ሃብት አለኝ ይላል። ይሁንና በእርግጥ ሃብቱ ያለበትን ደረጃ፣ ጥቅም የሚሰጥ ነው ወይንስ የማይሰጥና በብልሽት የተቀመጠ የሚለው የሚታይበት ሁኔታ የለም።
የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ስርዓት በአግባቡ መመራት እና የቦርዱ መቋቋም ያለው ፋይዳ
አቶ ደመላሽ እንደሚሉት፤ ምቹ የቢዝነስ አካባቢ ለኢኮኖሚ ማደግ ከፍተኛ ሚና አለው። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገና አገሪቱም ወደ ዓለም ገበያ እየገባች ነው። የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በእጅጉ እየጨመረ ነው። ይህ ለኢኮኖሚው ትልቅ ሃይል ቢሆንም በአግባቡ መቆጣጠርና መምራት ካልተቻለ ችግር ይዞ ይመጣል።
እንደ አገር ከኢንቨስትመንት ማግኘት ያለብንን ገቢ እንድናገኝ የሚያስችል የአሰራር ስርዓት ከሌለን ባለሃብቶቹ ያመጡትን መዋለ ንዋይ መልሰው የሚወስዱበት ሁኔታ ይፈጠራል። በመሆኑም የፋይናንስ ሪፖርት ስርዓታችንን በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢኮኖሚ እድገቱን መደገፍ በሚችል ደረጃ መቃኘት ይኖርብናል፡፤
ሙስና የሚመጣው ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት ከሌለ ነው የሚሉት አቶ ደመላሽ፣ የቁጥጥር ስርዓት ከሚገለፅባቸውና የሙስናን በር ከሚያጠቡ መንገዶች አንዱ ጠንካራ የፋይናንስ የአሰራር ስርዓት መሆኑን ያብራራሉ። የፋይናንስ የአሰራር ስርዓት በጠነከረ ቁጥር የግለሰቦች መደበቂያ እያነሰና እየጠፋ ይመጣል ይላሉ። ለዚህም ቦርዱ ትልቅ አገራዊ ፋይዳ እንደሚኖረው ይጠቁማሉ፡፡
እንደ አቶ ደመላሽ ማብራሪያ፤ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ታላላቅ አገራዊ ግቦች ፣ ሜጋ ፕሮጀክቶች ተቀርፀዋል። ከዚህ በተጓዳኝ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ይታሰባል። ይህ ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ የአገር ውስጥ ሃብት ማፍራትና በአግባቡ መጠቀምን ይጠይቃል። በዚህ መልክ ለማንሸፍነው ደግሞ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ወሳኝ ነው።
እነዚህን ለማግኘት በመሰረታዊነት መከናወን ካለባቸው ተግባራት መካከል የአገር ውስጥ ሃብትን ለማሰባሰብ የታክስ አሰባሰብ ስርዓቱን ማጠናከር፣ ጥራት ያለው አስተማማኝ፣ ግልፅ፣ ወጥነት ያለውና ሁሉም በቀላሉ ሊረዳው የሚችል የፋይናንስ ሪፖርት ማቅረብ የሚሉት ይገኙበታል። ቦርዱ ይህ እንዲመጣ ይሰራል።
የፋይናንስ ሪፖርት እና ኦዲት አቀራረብ አዋጅ እነማንን ይመለከታል?
አዋጁ አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችን እና በመንግስት በጀት የሚተዳሩ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን አይመለከትም። በንግድ ተግባር በተሰማሩ የግልም ይሁኑ የመንግስት ድርጅቶች ላይ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ማህበራትና ተመሳሳይ ሀላፊነት ያለባቸው ድርጅቶችንም ይመለከታል።
የቦርዱ ሃላፊነት እስከ ምን ድረስ ነው ?
እንደ አቶ ደመላሽ ገለጻ፤የመጀመሪያው ተግባሩ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃዎችን ማውጣት ሲሆን፣ ከእነዚህም አንዱ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃ ነው። ሁለተኛው የኦዲት ጥራትና የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብና አዘገጃጀት ግምገማና ክትትል ማድረግ ነው፤ ይህም በደረጃዎች መሰረት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን መከታተል ማለት ነው። የሙያ ትምህርት ስልጠናና ማጎልበቻ፤ የብቃት ማረጋገጥ እና እውቅና የመስጠት ተግባር ሌላኛው ነው። የምርመራና ህግ የማስከበር ተግባራትንም ያከናውናል፤ ይህም አንድ አራተኛ የሚሆነውን የአዋጁን ክፍል ይይዛል፡፡
በተቀመጠው ደረጃና ህግ መሰረትም እያንዳንዱ የንግድ ድርጅት እንደአቅምና ደረጃው የፋይናንስ እና የኦዲት ሪፖርቱን ለቦርዱ ያቀርባል። የቦርዱ ባለሙያዎች የቀረቡላቸውን ማስረጃዎች አገሪቱ ባስቀመጠችው የሪፖርት አቀራረብ ደረጃ መሰረት የተሰራ መሆኑን ይገመግማሉ፤ ያረጋግጣሉ። ሪፓርቱ ደረጃውን ካልተከተለ እንዲያሻሻሉ ጊዜ ይሰጣቸዋል። ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ካልሆኑ በወንጀል ይጠየቃሉ፤ አስተዳደራዊ እርምጃም ይወሰድባቸዋል፡፡
የአዋጁ መተግበር ለውጥ ያመጣል
ቦርዱ በተለይ ወቅቱ የሚጠይቃቸው ዓለም ዓቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃዎች በአግባቡ እንዲተገበሩ ሲያደረግ ከፍተኛ ጥራት ያለው የፋይናንስ ሪፖርት መውጣት ይጀምራል። የሂሳብ መረጃዎች የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው ይወጣሉ።
እንደ አቶ ደመላሽ ገለጻ፤ ይህ ከግብር አንጻር ቢታይ የአንድን ድርጅት ትክክለኛ ሃብትና እዳ እስከዛሬ ካለው በተሻለ ሁኔታ ለማወቅ ያስችላል። ምን ያህል መክፈል እንዳለበት የድርድር ጉዳይ አይሆንም። ምክንያቱም ደረጃዎቹ በግልፅ እንዲያስቀምጥ የሚጠይቁት አለና።
ይህን ተከትሎ ስለመሰራቱ ደግሞ ቦርዱ ክትትል ይደርጋል። እያንዳንዱ ድርጅት ለገቢዎች እንዲሁም ለባንክ ብድር የሚያስገባው ቦርዱ ዘንድ ባስመዘገበው የፋይናንስ መግለጫ መሰረት ነው። እንደ ከዚህ ቀደሙ ለባንክ ብድር ሲፈለግ ትርፋማ ፣ ለገቢዎችና ጉምሩክ ሲፈልግ እንደከሰረ አርጎ የሚያሳየው አካሄድ አሁን ቦታ አይኖርም።
ይህ መግለጫ የሚመዘገበውም በቦርዱ ነው፡፡ ወደ ገቢዎች ታክስ የሚወሰድበት መግለጫ ቦርዱ በመዘገበው መሰረት የሚከናወን ይሆናል። እንደ አስፈላጊነቱ የሚገለባባጥ ነገር አይኖርም። ከዚህ ቀደም አንድ ቢሊየን ብር የሚያወጡ ማሽኖችም ሆነ ሌሎች ቁሳቁስ አሉኝ በሚል ብድር መውሰድ ይቻል ነበር፤ አሁን መግለጫዎችን ማቅረብ የግድ በመሆኑ አሉኝ የሚባሉ እሴቶች ተገምገመው የሂሳብ መግለጫ ውስጥ የማይገቡ ከሆነ አበዳሪዎች ይጠነቀቃሉ።
ከዚህ ቀደም ባለሙያዎች ሂሳብ ሲያዘጋጁ አንዳንድ ችግሮች ቢከሰቱ ድርጅቱ አልያም ባለቤቱ ይጠየቃል እንጂ ባለሙያው ላይ ተጠያቂ አይሆንም፤ አሁን የሂሳብ ስራ መስራት ያለበት ማነው? የሚለው ደረጃዎችና ዝርዝር መመዘኛዎች ስለተቀመጡለት የሂሳብና የኦዲት አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎች እነማን ናቸው? ምን አይነት የትምህርት ዝግጅትና የስራ ልምድ ሊኖራቸውስ ይገባል? የሚለውም ተቀምጧል። ከደረጃ ውጪ የሰራ ካለም በግለሰብ ደረጃም እርምጃ ይወሰዳል በማለት አቶ ደመላሽ ያብራራሉ።
አቶ ደመላሽ እንደሚሉት፤ ከዚህ ቀደም የንግድ ድርጀቱ ባለቤት እንደዚህ አድርገህ አዘጋጅልኝ ብሎ የሚያዝበት ሁኔታ ነበር፤ አሁን ደረጃው በሚጠይቀው አግባብ እንጂ ነጋዴው በፈለገው አይፈጸምም። ባለሙያዎች በፈለጉት ስፍራ ሆነው በተጠየቁት መሰረት የሚሰሩበት መንገድ እንዲቀር እየተደረገ ነው። አንዱ ቢሮ ከፍቶና ብዙ ባለሙያዎች ቀጥሮ ለመንግስት ተገቢውን ግብር እየከፈለ ሌላኛው በተቃራኒ የሚሰራበት ሁኔታ መቅረት ይኖርበታል። እያንዳንዱ ባለሙያ ተመዝግቦ በተደራጀ መልኩ ቢሮ ከፍቶ እንዲሰራና የሰራበትን የተሟላ መረጃ እንዲይዝ በአጠቃላይ አገር፤ ባለሙያ እና ድርጀቶች ተገቢውን ጥቅም የሚያገኙበት አሰራር እንዲመጣ እየሰራን ነው።
ለቦርዱ የተሰጡት ተግባራት በማስፈፀም ረገድ የባለሙያ አቅም እንዴት ይገለፃል?
በአገራችን ውስጥ እነዚህን በተለይ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃዎችን ለመተግበር የሚያስችል በቂ እና አቅም ያለው ባለሙያ የለም። ስለ ሙያው ያለው ግንዛቤ በጣም ውስን ነው። እያንዳንዱ አካውንታንት በብሄራዊ ኢኮኖሚው ላይ ያለው አስተዋፆኦ አይታወቅም።
የዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎችም ስለዓለም አቀፍ ደረጃዎች አልተማሩም ። ተመራቂዎቹ ስለ ዓለም ዓቀፍ ደረጃዎች እንዲያውቁ ፣ትምህርት ተቋማት ያሉትም በቂ ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ ትልቅ ስራ ይጠይቃል። በመሆኑም ከፍተኛ የትምህርትና ማስልጠኛ ተቋማት ገበያው የሚፈልገውን የሰው ሃይል እንዲያምርቱ፤ ትምህርቱም በስርዓተ ትምህርት እንዲካታትና በዓለም ዓቀፍ ደረጃዎች እንዲቃኝ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ይገልጻሉ።
በእርግጥ በአሁኑ ወቅት ማንኛውም ሰው መሰልጠን ቢፈልግ በአቅራቢያው በሚገኝ ዩኒቨርሲቲና የግል ስልጠና ተቋም መሰልጠን ይችላል። በዚህም ባለሙያዎቹ ለዓለም ዓቀፍ መስፈርቶች ያላቸው ግንዛቤ እያደገ ነው። የማሰልጠኛ ተቋማትም ዓለም ዓቀፍ መስፈርቶቹን መሰረት ያደረገ ስልጠና መስጠት መጀመራቸውን የሚያበስር ማስተወቂያ እየሰሩ ናቸው።
በማስፈፀም ረገድ የክልሎችና የፌዴራል መንግስት ግንኙነት
አቶ ደመላሽ በፋይናንስ አቀራረብና የኦዲት ሪፖርት አዋጁ ላይ የተመለከተውን ጠቅሰው እንዳሉት ፤አዋጁ በመላ አገሪቱ ተፈፃሚ ይሆናል፤ አዋጁን ለማስፈፀምም ቦርድ እንደሚቋቋም በተገለጸው መሰረት ቦርዱ ተቋቁማል፤ ቦርዱ እንዲያስፈጽም ከተሰጡት ተግባራት መካከል የሂሳብና የኦዲት ባለሙያዎች የሙያ ነፃነትን ማስጠበቅ የሚለው ይገኝበታል። ይህም ወደ ሙያው ማነው መግባት ያለበት? የሚለውን ስለሚያካትት ለዚህ መመዘኛ በማስቀመጥ ለሚያሟሉ ፈቃድ የመስጠት ሃላፊነት ለቦርዱ ተሰጥቷል።
በህገ መንግስቱ የፌዴራልና የክልል መንግስታት በማለት ሁለት እርከኖች አሉ። የክልል መንግስታት በክልላቸው ውስጥ እንዲሰሩ የተፈቀደላቸው ተግባር ያለ ሲሆን የክልል ምክር ቤቶች ለክልል ዋና የኦዲት መስሪያ ቤቶች የኦዲትና የሂሳብ ሙያን የመቆጣጣር ስልጣን ሰጥተዋቸዋል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር የፋይናንስ ሪፖርት አዋጁ ሲወጣና ቦርዱ ሲቋቋም ይህን ስራ አቁሟል። በተወሰኑ ክልሎች ግን አይሆንም፤ ህገ መንግስቱ በሚፈቀድው መሰረት የክልሉ ምክር ቤት ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ሲቋቋም ለዋና ኦዲተር የሰጠው ስራ ነው። ፈቃድ መሰጠት ደግሞ በክልል ደረጃ የሚሰራ ስለሆነ ህገ መንግስታዊ መብታችን ይነካል። ስለዚህ ማስተካከያ መደረግ አለበት የሚል አጃንዳ አነሱ። ባለሙያዎችን ስንመዘግብ ከተወሰኑ ክልሎች መጥተው መመዝገብ አልቻሉም። ይህ ስራ የእኛ ስለሆነ በእኛ ነው የሚመራው የሚል አዝማሚያ ነበር። አሁን እነዚህ አዝማሚያዎች እየቀነሱ ሄደው ችግሩን ወደ መፍታት እየደረስን ነው።
ይህን ጥያቄ ለማስተናገድ መድረኮች ተዘጋጅተው፤ በመንግስትና በከፍተኛ ደረጃ ምክክር ተደርጎ የአዋጅ ማስተካከያ ተዘጋጅቶ ለሚኒስተሮች ምክር ቤት ተልኳል።በእርግጥ ይህ ችግር ለቦርዱ ትልቅ ፈተና እና እንቅፋት ሆኖበት ነበር።

ታምራት ተስፋዬ

Published in ኢኮኖሚ

የስፔኑን ጠንካራ ክለብ አትሌቲኮ ማድሪድንና የጀርመኑን ቦርሽያ ዶርትሙንድን በምድብ ማጣሪያዎች ወደ ዩሮፓ ሊግ ያወረደና በምድብ ማጣሪያ ከነበሩ 32ክለቦች 16ቱን ያሰናበተው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ከሁለት ወር በኋላ ዛሬና ነገ ጠንካራ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎችን ያስተናግዳል።በጥሎ ማለፉ ከሚገኙት 16 ክለቦች ስምንቱ ዛሬና ነገ ሲፋለሙ የቼልሲና ባርሴሎናን ጨዋታ ጨምሮ ቀሪ ስምንት ክለቦች የሚያደርጉት ጨዋታ በመጪዎቹ ማክሰኞና ረቡዕ ይካሄዳሉ።

ዛሬ ምሽት አራት ሰዓት ከ45 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መሪው ማንቸስተር ሲቲ ወደ ስውዘርላንድ በማቅናት ባዜልን ይገጥማል። የጣልያን ሴሪኤ ሻምፒዮን ጁቬንቱስ በሜዳው የሰሜን ለንደኑን ክለብ ቶተንሃምን ያስተናግ ዳል።
ረቡዕ ምሽት በተመሳሳይ ሰዓት በጥሎ ማለፉ ትልቅ ግምት የተሰጠው ሪያል ማድሪድና ፓሪስ ሴንት ዤርሜይን የሚያደ ርጉት ጨዋታ በግዙፉ የሪያል ማድሪድ ስታድዬም ሳንቲያጎ በርናባው ይካሄዳል።በሌላ የምሽቱ መርሐ-ግብር ሊቨርፑል ወደ ፖርቹጋል ተጉዞ ከፖርቶ ጋር ይጫወታል።

በሪሁ ብርሃነ

Published in ስፖርት
Tuesday, 13 February 2018 17:09

የሲቲ ካፑ ማሳረጊያ

የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በገቢ ራሱን ለማጠናከር፣ክለቦች ራሳቸውን እንዲፈትሹና ተጫዋቾቻቸውን የሚያስተዋውቁበት ዕድል ለመፍጠር የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድርን በየዓመቱ እንደሚያካሂድ ይታወቃል።ዘንድሮ በዓመቱ መጀመሪያ ላይ የተካሄደው 12ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር የተዋጣለትና ፌዴሬሽኑ ያልጠበቀውንና በሲቲካፑ ውድድር ታሪክ ሪከርድ የሆነ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ የተገኘበትም ነው።
ስድስት የአዲስ አበባ ክለቦችና ሁለት ተጋባዥ ክለቦች ከመስከረም 28 እስከ ጥቅምት 12 ቀን 2010 ድረስ የተፋለሙበት ይህ ውድድር በመጨረሻው የዋንጫ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናንና ቅዱስ ጊዮርጊስን አገናኝቶ በቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ አሸናፊነት መጠቃለሉ ይታወሳል።
ፌዴሬሽኑ ባለፈው ቅዳሜ ምሽት በከተማዋ ለሚገኙ ተሳታፊ ክለቦች ከውድድሩ ገቢ ድርሻቸውን ያከፋፈለበትን የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት በጁፒተር ሆቴል አካሂዷል። በሥነ-ሥርዓቱ ፌዴሬሽኑ ለተለያዩ አካላት እውቅና ከማበርከቱ ባሻገር ለታላቁ የህዳሴ ግድብ የገዛውን የ100 ሺ ብር ቦንድም ለአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስረክቧል። የክለቦቹ ተወካዮች በበኩላቸው ክለቦች በቅድመ ውድድር ራሳቸውን የሚመለከቱበት መልካም አጋጣሚ እንደሚሰጣቸው ያስረዳሉ።
የፌዴሬሽኑ ጊዜያዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ በለጠ ዘውዴ እንደተናገሩት፤ፌዴሬሽኑ በከተማዋ ለሚገኙ የሲቲ ካፑ ተሳታፊ ስድስት ክለቦች ከአንድ ሚሊዮን አራት መቶ ሺ ብር በላይ አከፋፍሏል።
በሥነ-ሥርዓቱ የውድድሩ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ 500 ሺ ብር በመውሰድ ቀዳሚ ሲሆን፣ በሁለተኝነት የጨረሰው ኢትዮጵያ ቡና 433 ሺ ብር ተረክቧል። ውድድሩን በሦስተኝነትና አራተኝነት ያጠናቀቁት ኢትዮ ኤሌክትሪክና መከላከያ ስፖርት ክለቦች እያንዳንዳቸው 133 ሺ ብር፣አምስተኛና ስድስተኛ በመሆን የጨረሱት የአዲስ አበባ ከተማ ስፖርት ክለብና ደደቢት ስፖርት ክለብ እያንዳንዳቸው 100 ሺ ብር ተረክበዋል።
የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በእግር ኳስ ውስጥ ባለፉ ሰዎች የተደራጀ መሆኑ አንድ የውድድሩ ስኬታማነት ምስጢር መሆኑን አቶ በለጠ ይናገራሉ። «ሕብረተሰቡ ስለውድድሩ በቂ መረጃ እንዲያገኝ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር የፈጠርነው ግንኙነትና ተጋባዥ ክለቦች ሻምፒዮን ከሆኑ ዋንጫውን መውሰድ ይችላሉ» የሚል አዲስ ደንብ ይዘን መቅረባችን ሌሎች የስኬቱ ምንጭ ናቸው» ሲሉ ሰብሳቢው ይገልጻሉ፡፡
በተለይ የደንቡ መሻሻል ተጋባዥ ክለቦች አሸናፊ ለመሆን እንዲጫወቱ ስላደረጋቸው ፉክክሩን ከሚጠበቀው በላይ አድርጎታል የሚል ሃሳብም ይሰጣሉ። በውድድሩ ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ውድድሮች ያልነበረው የጨዋታው ኮከብ ተጫዋቾች ምርጫ መደረጉ ለውድድሩ ድምቀት የራሱ አስተዋፅኦ እንደነበረው ይገልጻሉ።
ክለባቸው በየዓመቱ የሲቲካፕ ውድድሩ ተሳታፊ መሆኑንና ውድድሩ ክለቦች በዝግ ጅት ሂደት እያሉ መካሄዱ ከአዳዲስና ነባር ተጫዋቾች ተሰላፊዎችን ለመለየት ዕድል እንደሚፈጥርላቸው የሚናገሩት የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ተጠባባቂ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው ዮሴፍ ፣የዘንድሮው ውድድርም የክለቡ ደጋፊዎች በትኩረት የተመለከቱትና ውጤቱም የሚደነቅ እንደሆነም ይናገራሉ።
አቶ ጌታቸው ክለቡ ካለፉት ዓመታት የተሻለ የገንዘብ ድርሻ ማግኘቱን ተናግረው፥በቀጣይ ክለባቸው ከውድድሩ ተሳትፎ የሚያገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እየተዘጋጀ መሆኑን ይጠቁማሉ።
የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ግርማ አስራት በበኩላቸው፣«የሲቲ ካፑ ውድድር በከተማዋ ለሚገኙ ክለቦች ወሳኝ ውድድር ነው፣በቅድመ ዝግጅት የሚገኙ የፕሪሚር ሊጉና ከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ ክለቦችን ተጠቃሚ ያደርጋል»ይላሉ።
አቶ ግርማ እንደሚያስረዱት፤ውድድሩ አዳዲስ ተጫዋቾች የሚታዩበት፣ነባር ተጫዋቾች አቋማቸው የሚገመገምበት ነው።ከዚህ ባሻገር በከተማዋ የሚገኙ ክለቦችን በአንድ መድረክ የሚያገናኝ ውድድር በመሆኑ ለከተማዋ የእግር ኳስ ዕድገት ወሳኝ ነው።በተለይ በቀጣይ አስሩም ክፍለ ከተሞች ለሚያቋቁሟቸው የእግር ኳስ ክለቦች መጠናከር እገዛው ተጠቃሽ ነው።
በሥነ-ሥርዓቱ ኢንተርናሽናል አርቢትር ባምላክ ተሰማና ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊድያ ታፈሰ በፌደሬሽኑ እውቅና ተሰጥቷቸዋል።ፌዴሬሽኑ በቅርቡ የጤና መጓደል አጋጥሟቸው በመታከም ላይ ለሚገኙት የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ ስዩም አባተ የእውቅና ሽልማትና የ10ሺ ብር ድጋፍ አድርጓል።
ፌዴሬሽኑ የዘንድሮውን ገቢ በከተማዋ እግር ኳስ ተኮር ሥራዎችን እንደሚያካሂድበት የፌዴሬሽኑ ጊዜያዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ በለጠ ዘውዴ ይጠቁማሉ።
እንደ አቶ በለጠ ማብራሪያ፤የተለያዩ የውስጥ ውድድሮችን የሚያካሂድባቸውን የጃን ሜዳ ቁጥር ሁለትና ሦስት ሜዳዎችን አስጠርጓል።የማዘውተሪያ ስፍራዎች እጥረትን ለመቀነስ ከከተማዋ ስፖርትና ወጣቶች ቢሮ ጋር በመተባበር ምቹ በማድረግ ውድድሮችን ለማስፋት በየክፍለ ከተማው ያሉት ሜዳዎችን ለማስተካከል እየተዘጋጀ ይገኛል።የዳኞችና የአሰልጣኞች ስልጠና በመስጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን አቅሙን ለማጠናከርም ሙያተኞችን ለመቅጠርም አስቧል።
የጊዜያዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ፣ፌዴሬሽኑ በ13ኛው ውድድር የሲቲካፑን ጥራት የሚያሳድጉ አዳዲስ ነገሮችን ይዞ ለመምጣት ማሰቡን ይናገራሉ።እርሳቸው እንደሚሉት፤ ፌዴሬሽኑ በሚቀጥለው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር የሌሎች አገራት እግር ኳስ ክለቦችን በመጋበዝ የውድድሩ ተሳታፊ ለማድረግ አስቧል።የሲቲ ካፑ ተጋባዥ የክልል ክለቦች ከስታዲየም ገቢ የገንዘብ ድርሻ እንዲያገኙ ለማድረግም አቅዷል።

በሪሁ ብርሃነ

Published in ስፖርት

አነጋገሩ በቀጥታ ለውሻ ባይሰራም ‹‹ውሻ በላበት ይጮኸል‹‹ ሲባል ይደመጣል፡፡ ለቅልውጥ የሄደበት ቤት ከተመቸው በዚያው ሊቀር የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ለማመልከት ነው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ውሻ እና ድመት አርቀው ቢጥሏቸውም ይቆዩ ይሆናል እንጂ ቤታቸውን ሳይረሱ ሊመለሱ ይችላሉ ይላሉ፡፡

ስካይ ኒውስ ሰሞኑን ያስነበበው ዘገባ እንዳመለከተው አንዲት ውሻ ከጠፋች ከ10 አመት በሁዋላ ወደ ቤቷ ተመልሳለች፡፡ ባለቤቶቿ የዋሻዋን መመለስ ከሞት የመመለስ ያህል ቆጥረውታል፡፡ አቢ ይተሰኘችው ይህች ውሻ በጥሩ ይዞታ ላይ እንደነበረች ሁኔታዋ እንደሚያመለክትም ተጠቁሟል፡፡ ባለቤቷ ውሻዋ በጥሩ ሁኔታ ስተቀለብ እንዲሁም ጤናዋም ሲጠበቅ የነበረ በማለት ተናግረዋል፡፡
የውሻዋ ባለቤት ዴብራ ሱዬርቬልድ እንደተናገረችው፤ ፔንሳልቫኒያ አፖሎ ከሚገኘው ቤቷ እንደወጣች በቀረችው ውሻዋ መጥፋት በእጅጉ አዝና ነበር ፡፡ ውሻዋ በቆዳዋ ውስጥ ማይክሮ ቺፕ የተቀመጣላት ስትሆን፣ይሁንና የደረሰችበት ሳይታወቅ ለአስር አመታት ቆይታለች፡፡
ሰሞኑን ወደ ከቀድሞ ቤቷ 10 ማይል ርቀት ላይ ስትዘዋወር መገኘቷን ባለቤቷ ተናግራ ፣በአካባቢው የሚገኙ የእንስሳት ተንከባከቢዎች የውሻዋን ቺፕ በመመልከት ለባለቤቷ ማስረከባቸውን አስታውቃለች፡፡ ውሻዋን ያገኘችው ሱዬርቬልድ ለትሪዩቡን ሪቪው ‹‹ ውሻዬ ከሞት የተመለሰች ያህል ተሰምቶ ኛል፤የጠፋች ጊዜ በእጅጉ አዝነን ነበር ›› ስትል ተናግራለች፡፡ውሻዋ ስሟን እንኳ እንዳልረሳችም ጭምር ተናግራለች፡፡
ይህች ጥቁር ውሻ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝና የት አካባቢ ተሰውራ እንደኖረች እስከ አሁንም የታወቀ ነገር እንደሌለ ዘገባው ያመለክታል፡፡ ባለቤቷ ግን ውሻዋ ጥሩ ተንከባካቢ እንደነበራት ከሁኔታዋ መረዳቷን ተናግራለች፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

Published in መዝናኛ

 ፊሊፒንስ በኮንትሮባንድ ንግድ ክፉኛ መቆጣቷን የቻይና ዜና አገልግሎት ዘገባ አመልክቷል፡፡ ሀገሪቱ ሰሞኑን በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገሪቱ የገቡ 30 የቅንጦት አውቶሞቢሎችን በአደባባይ አውድማለች፡፡ በሀገሪቱ የጉሙሩክ መስሪያ ቤት በተካሄደ ተሽከርካሪዎቹን የማውደም ስነ ስርዓት ላይ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሮዲሪጎ ዱቴርቴ ም ተገኝተዋል፡፡ እነዚህ ግምታቸው አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የቅንጦት አውቶሞቢሎች ሀገሪቱ ምንም አላሳሳ ቻቸውም፡፡ በጨረታ ለመሸጥ ወይም ለሌላ አገልግሎት እንዲውሉም አልተፈለገም፡፡ እስከነተሸከሙት ገንዘብ ዶዘር እንዲወጣባቸው እንዲሁም በኤክስካቫተር እንዲዘነጣጠሉ በማድረግ እንዲወድሙ ሆነዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር

Published in መዝናኛ
Tuesday, 13 February 2018 17:04

የ‹‹አይፎኑ›› ጣጣ

ብዙ ጊዜ ተንቀሳቃሽ ስልኮቻችን ከእጃችን አምልጠው መሬት ላይ ሲወድቁ የመሰበር እድል ቢገጥማቸ ውም ቢያንስ የማስጠገኑና ዳግም በእጃችን የማስገባቱ እድል ይኖረናል፡፡ ከእጃችን አምልጥው መፀዳጃ ቤት የሚገቡ ስልኮችን ግን ምን ልናደርግ እንችላለን?
ኦዲቲ ሴንትራል የተሠኘው ድረ ገፅ ባሳለፈነው አርብ ለንባብ ያወጣው ፅሁፍ እንደሚያሳየው የእርሶ ስልክ መፀዳጃ ቤት ቢገባ እንዴት ማውጣት እንደሚችሉ የሚመክር ሳይሆን እንደውም እጅዎን አጣጥፈው እንዲቀመጡ የሚያሳስብ ይመስላል፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፤ ታንግ የተሰኘው ቻይናዊ የጉዋንዚ ክልል ነዋሪ ከጓደኞቹ ጋር በአካባቢው በሚገኝ አነስተኛ ሆቴል ውስጥ መጠጥ እየጠጣ ባለበት ወቅት መፀዳጃ ቤት መሄድ ያስፈልገዋል:: ወደዛውም ያመራል፡፡ በመፃዳጃ ቤቱ ውስጥ እያለ ስልኩን ማየት ይፈልጋል:: ሰውየው ግን ትንሽ ሞቅ ብሎት ኖሮ ውዱ አዲሱ አይ ፎን ስልኩ ከእጁ አምልጦ መፃዳጃ ቤት ቀዳዳ ውስጥ ይገባል፡፡
ታንግ አይፎን 8 የተሰኘውን ስልኩን ገና በቅርቡ እንደገዛውና 8 ሺ ወይም ደግሞ 1 ሺ 300 የአሜሪካን ዶላር እንዳወጣበት ዘገባው ገልፆ፤ ስልኩ ወደ መጸዳጃ ቤቱ በገባበት ቅፅበት ጎንበስ በማለት እጁን ወደ መጸዳጃ ቤቱ ቀዳዳ ይሰዳል፡፡ ስልኩ ላይ መድረስ ባለመቻሉም እጁን እስከ ትከሻው ድረስ ወደ ውስጥ ይለቀዋል፡፡ታንግ ስልኩ ላይ በእጁ ለመድረስ እንዳልቻለና ይልቁንም እጁ እዛው የመፀዳጃ ቀዳዳ ውስጥ ተሰንቅሮ እንደቀረ ይረዳል፡፡
ሰዎች እርዳታ እንዲያደርጉለት ጥሪ ማድረጉ በጣም አሳፋሪ መሆኑን የተረዳው ታንግ፣ እጁን ከመፀዳጃ ቤቱ ቀዳዳ ለማላቀቅ 20 ደቂቃ ፈጅቶበታል፡፡ ይሁን እንጂ እጁ የባሰ እየተጣበቀ በመሄዱ ከቀዳዳው ውስጥ ለመውጣት እርዳታ የግድ እንደሚያስፈልገው ይረዳል፡፡ ኩራቱንና እፍረቱን ወደጎን በመተውም የእርዳታ ጥሪ ማቅረብ ይጀምራል፡፡ ይህን የእርዳታ ጥሪ የሰማው የፅዳት ሰራተኛ ወደ መፀዳጃ ቤቱ በማምራት ታንግን ይመለከተዋል፡፡ ወዲያውም ለአካባቢው የድንገተኛ አደጋ ክፍል ስልክ ይደውላል፡፡
ዘገባው ሲቀጥልም የአደጋ ተከላካይ ሰራተኞች የታንግን እጅ ከመፀዳጃ ቤቱ ቀዳዳ ለማላቀቀ መቀመጫውን እስከ መፈንቀል ደርሰዋል ይላል ዘገባው፡፡ የአደጋ ተከላካይ ሰራተኞች የታንግን እጅ ከቀዳዳው ማላቀቅ የቻሉ ቢሆንም ውዱን አይ ፎን 8 ስልክ ግን ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ምስጋና ታንግ ለተዝናናበት ሆቴል ይግባና ሆቴሉ ታንግ ለደረሰበት ጉዳት ካሳ የሚከፍለው በመሆኑ ዳግም የአይፎን 8 ስልኩን ገዝቶ በእጁ ያስገባል ሲል ዘገባው አጠናቋል፡፡

 አስናቀ ፀጋዬ

Published in መዝናኛ

የኢትዮጵያ ጤና መድን ኤጀንሲ በአመዛኙ የአርሶ አደርና አርብቶ አደር የሕብረተሰብ ክፍሎች የጤና ተጠቃሚነትን ለማበረታታት እንዲያስችል ከ2003 ወዲህ በሃገሪቱ የገጠር ክፍሎች ስለተተገበረው ማሕበረሰብ አቀፍ የጤና መድን አገልግሎት በቅርቡ ለጋዜጠኞች እና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ በማሕበረሰብ አቀፍ የጤና መድን አገልግሎት ምንነትና አስፈላጊነት እንዲሁም ማሕበረሰብ አቀፍ የጤና መድን አገልግሎት ትግበራ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝና በመድኑ ተጨማሪ ወረዳዎችን ለማካተት እየተደረገ ስለሚገኘው ዝግጅት የቀረቡትን ማብራሪያዎች እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል።
የማሕበረሰብ አቀፍ መድን አገልግሎት አስፈላጊነት
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ ከሠሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት 11 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የጤና ወጪውን መክፈል ባለመቻሉ የተነሣ ብቻ በጤና ተቋማት አይገለገልም፡፡በዓለም ላይ ከ10 በመቶ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ለህክምና በሚያወጡት ወጪ ብቻ በቀጥታ ወደ ድህነት ይገፋሉ፡፡አገራት ከህመም በፊት በሚደረግ አነስተኛና ተከታታይ መዋጮ ሰዎች ህመም ሲያጋጥማቸው የህክምና አገልግሎት ያለክፍያ የሚያገኙበትን የጤና መድን ስርዓት በመዘርጋት ከዚህ ችግር መውጣት ችለዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት አንድ ሰው በዓመት ሶስት ጊዜ የጤና ተቋማትን መጎብኘት እንደሚኖርበት ያስቀምጣል፡፡ በኢትዮጵያ ግን በአማካይ አንድ ሰው ወደ ጤና ተቋማት የሚሄደው በሦስት ዓመት ሁለት ጊዜ ነው፡፡ይህም ከስታንዳርዱ አምስት እጥፍ በታች ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የሕክምና ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ መምጣት፣ የግንዛቤ ችግሮች እና በህክምና ወቅት የሚጠየቀው ያልተጠበቀ የህክምና ወጪ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያም ህብረተሰቡ ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ባለማግኘት ሳቢያ ሊደርስበት የሚችለውን ችግር በዘለቄታዊ ለመፍታት መንግስት የጤና መድን ኤጀንሲን በአዋጅ ቁጥር 191/2003 በማቋቋም የማሕበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ስርዓትን ተግባራዊ አድርጓል።
ማሕበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ከህብረተሰቡ፣ ከመንግስት እና ከሌሎች ምንጮች ሀብትን በማሰባሰብ እና በህብረተሰቡ መካከል የእርስ በእርስ መደጋገፍ ስርዓትን በመፍጠር ተጠቃሚው የጤና አገልግሎት በሚሻበት ወቅት አብዛኛውን ከኪስ የሚከፈል ወጪ በማስቀረት ፍትሐዊ፣ጥራት ያለው እና ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ሽፋን ቀጣይነት ባለው መልኩ የሚያገኝበት ስርዓት ነው።በገጠርና በከተሞች አካባቢ መደበኛ ባልሆነው ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ፣በተናጠል ሊፈጠር የሚችለውን ከፍተኛ የጤና ወጪ ጫና ማስቀረት እና በከፍተኛ የጤና ወጪ ምክንያት ቤተሰቦች ወደ ከፋ ድህነት እንዳይገቡ ለማድረግም ተመራጭ መፍትሔ ነው።
የማሕበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ሙከራ ትግበራና የደረሰበት ሽፋን
በ2003 ዓ.ም የማሕበረሰብ አቀፍ ጤና መድን የሙከራ ትግበራ መመሪያ ከወጣ በኋላ 2004 ዓ.ም ላይ በኦሮሚያ፣ትግራይ፣አማራና ደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በተመረጡ አስራ ሶስት ወረዳዎች የሙከራ ትግበራ ተካሂዷል።በ13ቱ ወረዳዎች የሙከራ ትግበራ የግምገማ ጥናት ከተካሄደ በኋላ ፥በ2008ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ የጤና መድን አገልግሎቱ እንዲስፋፋ ተደርጎ በ201 ወረዳዎች እንዲጀመር ተደርጓል።ይህ አገልግሎት በአሁኑ ወቅት በ289 ወረዳዎች እየተሰጠ ይገኛል፡፡
አገልግሎቱ በከተሞችም መደበኛ ባልሆነ ክፍለ-ኢኮኖሚ ህይወታቸውን የሚመሩና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የከተሞች ነዋሪዎችን ጭምር ተጠቃሚ ለማድረግ እየተስፋፋ ነው ።ለዚህም በአዲስ አበባ ከተማ ለሙከራ በተመረጡ 10 ወረዳዎች ባለፈው ህዳር ወር አገልግሎቱ በይፋ ተጀምሯል።
አመታዊ የአባልነት መዋጮ መጠንና የሚሸፈኑ አገልግሎቶች
በአሁኑ ወቅት የማሕበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አባልነት በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ሲሆን አባል መሆን የሚቻለው በቤተሰብ ደረጃ ነው፡፡ መዋጮ የከፈለ ወይም የተከፈለለት አባወራና እማወራ እንዲሁም መክፈል የማይችሉ እማ/አባወራ ሙሉ በሙሉ አባል ይሆናሉ። አገልግሎቱ ከሙከራ ትግበራ በኋላ ዓመታዊ ክፍያው ከነበረበት 132 ብር በገጠር የሚገኙ አባላት 240 ብር በዓመት ከፍለው እንዲገለገሉ ተደርጓል። በገጠር ከተሞች የሚኖሩ ተጠቃሚዎች ደግሞ 350 ብር በመክፈል አባል መሆን ይጠበቅባቸዋል። አገልግሎቱ በቀጣይ በትልልቅ ከተሞች ሲስፋፋ አመታዊው የአባልነት ክፍያ 500ብር እንዲሆን ተወስኗል።በሂደትም የገቢ መጠንን ያገናዘበ የመዋጮ መጠን እንደሚተገበር 2008 ዓ.ም በወጣው የማስፋፊያ መመሪያ ላይ ሰፍሯል።
የጤና መድኑ ስራ በጀመረባቸው ወረዳዎች ላይ የሚገኙ ተገልጋዮች የመድን አገልግሎት እንዲሰጡ ውል ባሰሩ ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች የተመላላሽ ሕክምና፤የተኝቶ ሕክምና፤የቀዶ ህክምና፤በሕክምና ባለሙያዎች የታዘዙ የምርመራ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ።
በማሕበረሰብ አቀፍ የጤና መድን የተገኙ ውጤቶች
በአገልግሎቱ በታቀፉ ወረዳዎች ከ15ሚሊዮን በላይ ህዝብ የጤና መድን ሽፋን አግኝቷል።የቤተሰቦች የጤና ወጪ ጫናን በመቀነስ ከከፍተኛ የጤና ወጪ መታደግ እየተቻለ ነው።የጤና መድኑ በተተገበረባ ቸው አካባቢዎች የሚገኝ ሕብረተሰብ የጤና አገልግሎት አጠቃቀም መጠኑ ጨምሯል። በቤተሰብ ደረጃ የሴቶችን ውሳኔ ሰጭነት በማጠናከር እናቶችና ህጻናት የጤና አገልግሎት ባስፈለጋቸው ጊዜ እንዲያገኙ አስችሏል።
የጤና አገልግሎት ጥራት ለማሻሻል ጭምር የራሱን ሚና በመጫወት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣መክፈል የማይችሉ የድሃ ድሃ አባላት የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ በማድረግ የጤና አገልግሎት ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማስፈን እገዛ እያደረገ ይገኛል።በተጨማሪም የዜጎች ተሳትፎም እንዲያድግ ያለው አስተዋጽኦ የጎላ ነው።
የጤና መድኑን የሚመጥን የጤና አገልግሎት ጥራት የማረጋገጥ ኃላፊነት
የማሕበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎቱ በተጀመረባቸው ወረዳዎች ጤና ተቋማትን ዝግጁ ማድረግ መሠረታዊ ጉዳይ በመሆኑ ኤጀንሲው፣ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ጤና ቢሮዎች በጋራ ተቋማቱን ለማጠናከር እየሠሩ ናቸው።የጤና ተቋማት የጤና አገልግሎት ጥራት ኮሚቴ ማቋቋም ጀምረዋል።በመላ ሀገሪቱ ጤና ተቋማት ከተደራሽነታቸው ባሻገር ተገልጋዮች የተሟላ አገልግሎት የሚያገኙባቸው ለማድረግ የማሻሻያ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።የሚያጋጥመውን የመድኃኒት አቅርቦት ችግር ለመፍታት ተጨማሪ ተሽከርካሪዎች ወደ ስራው እንዲገቡ እየተደረገ ነው፥መጋዘኖችም እየተስፋፉ ይገኛሉ።ከዚህ በተጨማሪ የመድሀኒት ስርጭት ስርዓቱን መለወጥ ያስፈልጋል።
ለዚህም የመድሀኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጄንሲ በድጋሚ ይዋቀራል።በእስካሁኑም የመድሃኒት አቅርቦቱ መሻሻሎች አሳይቷል።ከጊዜ ወደ ጊዜ የሃኪሞች ቁጥር እየጨመረ ነው።አሁን በየወረዳው የሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ጠቅላላ ሀኪሞች አሉዋቸው።ጤና ባለሙያዎችን ብቃት ማሳደግ አንዱ የጤናው ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አጀንዳ ሲሆን ርህሩህ፣ተንከባካቢና አክባሪ ሐኪሞችን ለመፍጠር አምባሳደሮች በመምረጥ እየተሰራ ይገኛል።
የጤና መድኑን ሽፋን የማሳደግ ውጥን
የጤና መድን አገልግሎቱ ባልተጀመረባቸው ክልሎች አገልግሎቱን ለማስጀመር የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ ሲሆን በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ሀረሪ እና ድሬዳዋ መመሪያ ጸድቆ የአባላት ቅስቀሳ እና የምዝገባ ስራ እየተከናወነ ነው።በኢትዮ ሶማሌ ክልል እና ጋም ቤላ ክልል የትግበራ መመሪያ ወጥቷል፣በአፋር ክልል መመሪያ ለማጽደቅ ዝግጅት እየተጠናቀቀ ይገኛል።
አገልግሎቱ በተጀመረባቸው ክልሎች በተያዘው ዓመት በ197ወረዳዎች የአባላት ቅስቀሳና የምዝገባ ስራ እየተሰራ ነው።የጤና ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን አካል የሆነው የወረዳ ትራንስፎርሜሽን ሲሆን አንድን ወረዳ ትራንስፎርም ለማድረግ በወረዳው በዚህ የጤና መድን መታቀፍ ያለባቸው ነዋሪዎችን የመድኑ አባል ማድረግ ሲቻል በመሆኑ ማሕበረሰብ አቀፍ የጤና መድኑ በ2012ዓ.ም መደበኛ ባልሆነ ክፍለ-ኢኮኖሚ የተሰማሩ ከ80-85 በመቶ ዜጎች እንዲያቅፍ ይጠበቃል።
በመድኑ የትግበራ ሂደት ያጋጠሙ ዋና ዋና መሰናክሎች
በየአስተዳደር እርከን ያለው አመራር አገልግሎቱን በተመሳሳይ የባለቤትነት ኃላፊነት በሁሉም አካባቢ ተመሳሳይ አለመሆኑ አንዱ መሰናክል ነው።ስርዓቱ አዲስ እንደመሆኑ መጠን በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆን ሌላኛው ፈተና ነበር።በሌላ በኩል የጤና ተቋማት ዝግጁነትና የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተት በትግበራ ሂደት ከታዩ ችግሮች አንዱ ነበር።

 በሪሁ ብርሃነ

Published in ማህበራዊ

ኢትዮጵያ ላለፉት አስራ አራት ዓመታት ገደማ በተከታታይ ባለሁለት አኃዝ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግባለች፡፡ በዚያው ልክ የዜጎች ተጠቃሚነት በመሰረተ ልማት ፣በትምህርት፣ በጤና እና በመሳሰሉት በኩል እየተረጋጋጠ ይገኛል፡፡ አንድ ሀገር የምግብ ዋስትናዋን ማረጋገጥ ችላለች፡፡ ሀገሪቱ ይህን እድገት ለማምጣት ባደረገችው ርብርብ በተመዘገቡ ስኬቶች የድህነትን ተራራ መናድ ጀምሯል፡፡
በግብርናው በኩል እየተካሄደ ያለው እንቅስቃሴ አገሪቱ እያስመዘገበች ለምትገኘው ለውጥ ከፍተኛውን ሚና እየተጫወተ ነው። የዘርፉ ምርትና ምርታማነት እያደገ መጥቶ የአርሶ አደሩም ተጠቀሚነት በዚያው ልክ እየጨመረ ነው፡፡
ኢኮኖሚውን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር እየተደረገ ባለው ርብርብ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢንዱስትሪ ዘርፉ የሚከናወኑ ተግባሮች ተበራክተዋል። በሀዋሳ ፣ ኮሞቦልቻ እና መቀሌ የተገነቡ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለዚህ በማሳያነት ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡
ለሁሉም እንቅስቃሴ ወሳኝ እየሆነ ለመጣው የኤሌክትሪክ ልማትም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡ ባለፉት 26 አመታት የተከዜ የጊቤ አንድ ፣ሁለት እና ሴ ሦስት ግደቦች ተገንብተዋል፤ የጣና በለስ እና በተለያዩ አካባቢዎች የንፋስ ሀይል ማመንጫዎች ተገንብተው ወደ ስራ ገብተዋል፡፡ በዚህም ሀይል የማመንጨት አቅም በ1984 አ.ም 379 ሜጋ ዋት ከነበረበት ወደ 4ሺ 200 ሜጋ ዋት ማድረስ ተችሏል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና ሌሎች ግድቦች እንዲሁም የንፋስ የእንፋሎት ፣እና የፀሐይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ ይገኛሉ፡፡ የኤሌክትሪክ ሀይል ልማቱ ሀገሪቱ ኢኮኖሚዋን ከግብርና ወደ ኦንዱስትሪ ለማሸጋገር ለምታደርገው ጥረት ሚናው ከፍተኛ ይሆናል፡፡
ኢህአዴግ አስረኛውን ድርጅታዊ ጉባኤ በመቀሌ ከተማ ባካሄደበት ወቅት የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ክላስተሮችን በስፋት በማልማትና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ኢንቨስተሮችን ለመሳብ የሚያስችል ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል፡፡ ይህ ውጥኑ በእነዚህና በሌሎች የኢንዱስት
ሪ ፓርኮች እውን እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህም ከቦታ ከመሰረተ ልማት እና ከተቀናጀ አሰራር ጋር በተያያዘ ዘርፉን ያጋጥሙት የነበሩ ችግሮችን መፍታት በማስቻሉ በተለይ የውጭ ባለሀብቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያለምንም ውጣ ውረድ ወደ ዘርፉ እንዲገባ አስችሏል፡፡
እነዚህ በመሰረተ ልማት፣ በግብርና በኢንዱስ ትሪ መስክ የተከናወኑ ተግባሮች ለአብነት ተጠቀሱ እንጂ ልማቱ በተለያዩ ዘርፎችም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ አገሪቱ እያከናወነቻቸው በምትገኘው እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድበ ያሉ ዘርፈ ብዙ ተግባሮች በርካታ የሚያስጎመጁ የልማት ተስፋዎች ባለቤት ሆናለች፡፡ ይሁንና በተከናወኑት ተግባሮች የኢትዮጵያውያን የዘመናት ባላጋራ ድህነት ቀነሰ እንጂ አልተወገደም፤ እንደ ሀገር የምግብ ዋስትና ተረጋገጠ እንጂ በቤተሰብ ደረጃ ገና ያልተሰሩ ስራዎች አሉ፡፡
እነዚህ ችግሮች ሳይፈቱ ሀገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሌሎች ችግሮች ፈተና ሆነውባታል፡፡ እያደገ የመጣው ኢኮኖሚዋ ያስከተለው ፍላጎት አለ፤ ህዝቡ ከመልካም አስተዳደር እጦት፣ ከሙስና ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር አያይዞ የሚያነሳቸው ቅሬታዎች በአናት በአናቱ እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ በየጊዜው የሚቀሰቀሱ ግጭቶች፣አለመግባባቶች የእነዚህ ችግሮች መገለጫዎች ናቸው፡፡ ግጭቶቹንና አለመግባባቶቹን በማራገብ የውጭ ሀይሎች እና የሀገሪቱ ጠላቶች ለከንቱ አላማቸው ሊጠቀሙባቸው እየቋመጡ ናቸው፡፡
የስራ አጡም ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መጥቶ ወጣቶች የስራ ያለህ የሚሉባት ሀገር ሆናለች፡፡ ወጣቶችን ከስራ አጥነት ለመታደግም መንግስት 10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ብድር ፈቅዶ የስራ እድል ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ ያለውም ለዚሁ ነው። የፓለቲካ ምህዳሩ መጥበብም ሌላኛው ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡
በሀገሪቱ በተለያዩ መስኮች ስኬቶች የተመዘገቡት ፈተናዎችን በማለፍ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሀገሪቱ በጸጥታና በደህንነት በኩል ፈተና አጋጥሟታል፡፡ በሀገሪቱ እየተመዘገበ ስላለው ለውጥና ስላጋጠው ስጋት እና መፍትሄ የተለያዩ የህብረተሰቦች ክፍሎች ምን ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ የድሮ ኢትዮጵያ አይደለችም›› የሚሉት የፌዴራል ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ መሀመድ አልሙባረክ ሼህ መሀመድ አወል፣ ሀገሪቱ አሁን ወሳኝ ሀገር መሆኗን ይገልጻሉ፡፡ በአፍሪካ ግንባር ቀደምና የአህጉሪቱ ቃል አቀባይ ናት፤ በልማትም ከመሪዎቹ ተርታ ተሰልፋለች ሲሉ ያብራራሉ፡፡
አጓጓጊ የልማት አጀንዳ ይዛ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች የሚሉት ሼህ መሀመድ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ለዚህ በአብነት ይጠቅሳሉ፡፡ ግድቡ መሰራት የለበትም፤ እንዴት ሲባል ነው በአባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ ግድብ የምትገነባው›› ከሚለው የማጣጣል ንግግር ተወጥቶ የግድቡ ግንባታ አሁን እዚህ ላይ መድረሱ በአድናቆት ሊታይ የሚገባው ነው ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያም በአባይ ወንዝ ይደርስባት ከነበረው ጫና ወጥታ የተፋሰሱን ጉዳይ በሶስትዮሽ ግንኙነት መመልከት የሚያስችል ሁኔታ ውስጥ እንደምትገኝ ጠቅሰው፣ ጉዳዩን በሰከነ መንገድ ማስኬድ መቻሏንም እንደ ታላቅ ስኬት ይመለከቱታል፡፡ ይህም በርካታ ውዝግብ ታልፎ የተደረሰበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ለአገሪቱ ስኬታማነት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ያስረዳሉ፡፡ እዚህ ስኬት ላይ ለመድረስ ያስቻላት በፖለቲካውም ሆነ በዲፕሎማሲው መስክ የተጫወ ተችው ሚናና ያላት ተደማጭነት መሆኑንም ያብራራሉ፡፡
መንግስት በርካታ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን እያካሄደ መሆኑን በመጥቀስም፣ በሌሎች አገልግሎት፣ በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖር ቱንና እንዲሁም በኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር አገልግሎትም የተከናወን ተግባር ይጠቅሳሉ፡፡ ልማቱ ከራሷ አልፎ ለጎረቤት አገራትም መነቃቃት እየፈጠረ ይገኛል ይላሉ፡፡
የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ናስር ካንሶ አገሪቱ በእስካሁኑ ሂደት በኢኮኖሚው በፖለቲካውና በማህበራዊው መስክ የተቀዳጀቻቸው በርካታ የሚያስጎመጁ ስኬቶች እንዳሉ ይጠቅሳሉ፡፡ እሳቸውም የመሰረተ ልማት ዝርጋታውን በመጥቀስ በመንገድ ልማት የተከናወኑ ተግባሮችን ያብራራሉ፡፡ ቀበሌዎችና የገጠር ወረዳዎች በመንገድ በኩል ከፍተኛ ችግር ያጋጥማቸው እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ችግሩ እየተቃለለ እንደሚገኝ ይገልጻሉ።
አቶ ናስር እንደሚሉት፤በግብርናው ዘርፍ ስኬታማ ተግባር ተከናውኗል፤ ይህም የአርሶ አደሩን ሕይወት መቀየር ያስቻለ ከመሆኑ በተጨማሪ ላለፉት 14 ዓመታት የኢኮኖሚ እድገቱ ባለሁለት አኃዝ እንዲሆን ካስቻሉት መካከል ግምባር ቀደሙ ነው።
አገሪቱ በርካታ ግንባታዎችን እያካሄደች ትገኛለች። ልማቷ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸር እየጨመረ መጥቷል። ለዚህ አንዱ ማሳያ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ነው፡፡ አገሪቱ ለዘመናት በቁጭት ስትንገበገብለት የኖረችው የአባይ ጉዳይ በህዳሴ ግድብ ግንባታ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ እያሸጋገረ ነው ።
በማህበራዊ ተቋማት በተለይም በትምህርት ተደራሽነት ላይ አመርቂ ተግባር ተከናውኗል፡፡ የትምህርት ጥራት ጉዳይ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ ቢሆንም ተደራሽነት ላይ ግን ብዙ ርቀት ተሄዷል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአንድ የገጠር ቀበሌ ውስጥ እስከ ሁለት ትምህርት ቤቶችን መክፈት፣ በዚህም ማንኛውም እድሜው ለትምህርት የደረሰ ታዳጊ በትምህርት ገበታ ላይ እንዲገኝ ማድረግ ተችሏል ።
በጤናው ዘርፍም ውጤታማ መሆን በመቻሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር እውቅና ማግኘት መቻሉን ይጠቅሳሉ። በዘርፉ የሚጠቀሱ ክፍተቶች እንዳሉም ይጠቁማሉ፡፡ በልብ፣ ኩላሊትና በመሳሰ ሉት ህክምናዎች ላይ የሚጠበቀውን ያህል አገልግ ሎት መሰጠት አለመቻሉን ጠቅሰው፣ በዘርፉ አሁንም ይበልጥ መስራት እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ።
አቶ ናስር ሌሎች የሚያስጎመጁ ድሎች ብለው ካነሷቸው መካከልም የአየር ትራንስፖርቱ እድገት ይገኝበታል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ውጤታማ ስለመሆኑ ለቀባሪው እንደማርዳት ይሆናል ያሉት አቶ ናስር፣ ተቋሙ ከስኬታማነቱ የተነሳ የሌሎች የአፍሪካ አገሮችን የአየር ትራንስፖርት ለማዘመንም እምነት የተጣለበት ለመሆን መብቃቱን ይጠቅሳሉ፡፡
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ ለትራንስፖርት አገልግሎት መብቃቱ፣ በምድር ባቡር በኩል የአገሪቱን የተለያዩ ክፍሎችንም ሆነ አገሪቱ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ለማስተሳሰር እየተካሄደ ያለው እንቅስቃሴ እንደሚያስጎመጁ ያብራራሉ።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽኑ አቶ ነጋ አደሬ በሀገሪቱ በልማት ደረጃ በርካታ ስኬቶች መመዝገ ባቸውን መጥቀስ እንደሚቻል ይናገራሉ፡፡ ለማሳያነትም አገሪቱ እያስመገበች ያለችውን ባለ ሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት ያመለክታሉ፡፡
እርሳቸው እንደገለጹት፤ አገሪቱ እያስመዘ ገበች ያለችው የኢኮኖሚ እድገት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያስጎመጀ መጥቷል፡፡ በኢንዱስትሪው መስክ ተገንብተው ባለሀብቶች እየገቡባቸው የሚገኙትን አሁንም እየተገነቡ ያሉት ፓርኮች አገሪቱ በኢንዱስትሪው ዘርፍ በትክክለኛው መስመር ላይ መሆኗን ያመለክታሉ፡፡ ኢንዱስትሪው ግብርናውን እንዲረከብ ሁኔታዎች እየተመቻቹ ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካም ሆነ በዓለም ላይ ከፍተኛ እድገት በማስመዝገብ ላይ ካሉ አገራት ተርታ መሰለፏን ይጠቁማል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ለአገሪቱ ምን ሊያመጣ ይችላል የሚለውን ከወዲሁ ማየት በራሱ አንዱ የሚያስጎመጅ ተግባር ነው የሚሉት አቶ ነጋ፣ ይህ ጥረት የመጣው በአንድ ጀምበር እንዳልሆነም ይናገራሉ፡፡ ሕዝቡ ለግንባታው ገንዘቡን፣ እውቀቱን ፣ጉልበቱን በአጠቃላይ ማንነቱን እንደሰጠም ጠቅሰው፣ ይህ በኢኮኖሚው ላይ የሚያመጣው ለውጥ በጣም ትልቅ እንደሆነም ያብራራሉ፡፡
ከዚህ ታላቅ ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ የተከናወነውን የዲፕሎማሲ ስራም ለግባታው ትልቅ አቅም መሆኑን በመጠቆም የሼህ መሀመድ አልሙባረክ ሼህ መሀመድ አወል እና የአቶ ናስርን ሀሳብ ያጠናክራሉ፡፡
የአቶ ናስርን ሃሳብ በማጠናከርም የአገሪቱ አየር ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሽ ተግባር እያበረከተ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ እንደ አቶ ነጋ ማብራሪያ፤ ይህ በአህጉር አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደሙን ስፍራ የያዘ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት በአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ላይ የራሱን አሻራ እያሳረፈም ነው፡፡ ለአገሪቱ ገጽታ ግንባታ የበኩሉን እየተወጣ ሲሆን፣ ኢንቨስትመንትን የመሳብ አቅሟ እያደገ እንዲመጣ እያደረገም ነው፡፡
አቶ ናስር አገሪቱ በቀረጸቻቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በመመራት ላለፉት ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ጊዜያት በርካታ ድሎችን ያስመዘገበች የመሆኗን ያህል ልታሳካቸው ያልቻለቻቸው ጉዳዮች እንዳሉም ይጠቁማሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ብሄራዊ መግባባትን ከመፍጠር አኳያ ውስንነቶችን መታየታቸውን፣ የፌዴራል ስርዓቱ መሰረቱ ህብረ ብሄራዊነት እንጂ ጎሰኝነት አለመሆኑ በሚገባ ግንዛቤ ያልተጨበጠበት መሆኑን በማመልከት ከዚህም አኳያ የሚታዩ የተዛቡ አመለካከቶች መኖራቸውን ያመለክታሉ፡፡
እንደ አቶ ናስር ማብራሪያ፤ ህገ መንግስቱን በተመለከተ ዜጎች ግንዛቤ እንዲጨብጡ ማደረግ ላይ እንዲሁም ህዝቡ ህገ መንግስቱን መረዳት ብቻ ሳይሆን መተግበርም እንዲችል በማድረጉ በኩል ውስንነቶች ይስተዋላሉ። ወጣቶችም፣ ሴቶችም ሆኑ ቀሪው የህብረተሰብ ክፍል መብቱንም ሆነ ግዴታውን ማጣጣም እንዲችል ሁኔታዎች በሚገባ አልተመቻቹም፡፡ ከዚህም የተነሳ ከፍተኛ ችግር እያጋጠመ ነው።
የዴሞክራሲ ስርዓት ከመገንባት አኳያ በተለይ የመድብለ ፓርቲን በማጠናከሩ በኩል ክፍተት ይታያል። ክፍተቱ ጥቂት ለማይባሉ ዜጎች የቅሬታ ምንጭ እየሆነ መጥቷል፡፡ ሌላው በዋናነት የሚጠቀሰው የመልካም አስተዳደር ችግር ነው። የመንግስት ተሿሚዎችና አመራሮች ድምጹን የሰጣቸውን ህዝብ በአግባቡ ማገልገል ሲገባቸው ራሳቸው ተገልጋይ ሆነዋል፡፡ ይህ ጉዳይ ህዝብን በከፍተኛ ደረጃ እያስቆጣ ነው፡፡
አቶ ናስር በፌዴራል ስርዓቱ ላይ ያለውን የግንዛቤ እጥረት የአገሪቱ ዋና ችግር በማለት ያብራራሉ፡፡ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውስጥ የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱን ከማሳደግ አኳያ የተሰጡ መብቶችን በትክክል እንዲጠቀሙ አለማድረግ፣ ህዝቡ የስልጣን ባለቤት ሆኖ እያለ የመልካም አስተዳደር ችግር በመፍጠር ህዝብን መበደል፣ ስልጣንን የህዝብ ማገልገያ ማድረግ ሲገባ የሀብትና ንብረት ማካበቻ አድርጎ የማየት ጉዳይን ዋና ዋና ችግሮች ብለው ያብራራሉ፡፡ ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት የሀገሪቱ ችግር ስለመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባልም ይላሉ።
በሀገሪቱ የተመዘገቡ ስኬቶችን አይቶ እንዳላየ ማለፍ ካልተፈለገ በስተቀር አገሪቱ የሚያስጎመጅ እድገት እያስመዘገበች እንደምትገኝ መረዳት አያስቸግርም የሚሉት አቶ ነጋ፣ ጎልተው የሚታዩ ውስንነቶች እንዳሉም በመጠቆም የአቶ ናስርን ሀሳብ ያጠናክራሉ፡፡ ‹‹ችግሮቹም በዋናነት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ናቸው›› የሚሉት አቶ ነጋ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮቹ በአብዛኛው መፈታት ሲችሉ ያልተፈቱ መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡ ከሙስና ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮች፣ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ድርጊት በስፋት መታየቱ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግር መባባሱ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት የሚያስገነዝቡ መሆናቸውን ይጠቁማሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች ከተወገዱ አገሪቱ ወዳቀደችው ከፍታ የማትምዘገዘግበት ምንም ምክንያት እንደሌለም ይጠቁማሉ፡፡
አቶ ነጋ አገሪቱ ከጎረቤት አገራት ጋር የተሻለ ግንኙነት እንዳላት ገልጸው፣ ኤርትራ አሁንም ችግር እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ በአሸባሪ ድርጅት የፈረጀቻቸውን አካላት በማስጠጋት በኢትዮጵያ ሰላም እንዳይኖር የማትፈነቅለው ድንጋይ እንደማይኖርም ይጠቁማሉ፡፡ የኤርትራ መንግስት በውስጡ የሚፈለፍላቸው ተቃዋሚ ሃይሎች የሽብር አጀንዳ ይዞ ይንቀሳቀሳል፡፡ በዚህም በርካታ ችግሮች ተፈጥረው አስተውለናል፡፡ ይህ ችግር ኢትዮጵያ ከህዝቧ ጋር ተቀራርባ በመስራት ትፈታዋለች የሚል እምነት እንዳላቸውና በዚህ አቅጣጫ መንግስትም ትልቅ ትኩረት መስጠቱን ያብራራሉ፡፡
እንደሚታወቀው መንግስት የፓለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እንደሚሰራ ካለፈው አመት አንስቶ እየሰራ ነው፡፡ በቅርቡም ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ እነዚህን ችግሮች ተረድቶ የልማቱም የዚህ ችግርም ባለቤት እኔ ነኝ በማለት ለመፍታት ከህዝቡ ጋር እንደሚንቀሳቀስ አረጋግጧል ፡፡
ገዥው ፓርቲ የፓለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የተያያዘውን ጥረት በተጨባጭ ለማረጋገጥ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ እየተደራደረ መሆኑ እንዳለ ሆኖ በቅርቡ የኢህአዴግ ማእከላዊ ኮሚቴ የፓለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በሚል ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ያሉ እንዲሁም ተፈርዶባቸው በእስር ላይ የሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችንና ሌሎችን በምህረትና በይቅርታ ለመፍታት በገባው ቃልና ህጉ በሚፈቅ ደው መሰረት በሺዎች የሚቆጠሩ ክሳቸው ተቋርጦ እየተፈቱ ናቸው፤ በይቅርታ እየተ ለቀቁ ይገኛሉ፡፡

አስቴር ኤልያስ

Published in ፖለቲካ

የደቡብ አፍሪካዋ ኬፕታውን ነዋሪዎች ሰሞኑን በጣለው ዝናብ በእጅጉ ተደስተዋል፡፡ ሁሉም ማለት ይቻላል ከየቤታቸው ወጥተው ዝናብ ውስጥ በመቆም ፈጣሪያቸውን ሲያመሰግኑ እንዲሁም ሲፈነጥዙ መታየታቸውን የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል፡፡
የ8 ሚሊ ሜትር መጠን ያለው ዝናብ በጉጉት ሲጠበቅ የቆየ እና ታላቅ የምስራችም ተደርጎ ተውስዷል። በቅርቡ የአገሪቱ የሚቲዮሮሎጂ ድርጅት በከተማዋ ዝናብ እንደሚጥል በለቀቀው መረጃ መሰረት ዝናብ መጣሉ ፣ነዋሪዎቹ አትክልታቸውን የሚያጠጡት፣ ለተጨማሪ የመጸዳጃ ቤት አገልግሎት እና ለሌሎች የጽዳት ተግባሮች የሚያውሉት ውሃ እንዲ ያጠራቅሙ ዕድል እንደሰጣቸው አስታውቀ ዋል፡፡ሌሎች ደግሞ ዝናቡ ገላቸውን በመንካቱ ብቻ ተደስተዋል፡፡አንዳንዶች ዝናብ ጣለ ተብሎ የሚሰጣቸው የውሃ አገልግሎት እንዳይስተጓጎል ስጋት እንዲያድርባቸው አድርጓል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች በከተማዋ ከታየው ድርቅ ጋር ተያይዞ ለከፍተኛ የውሃ ችግር ተዳርገው የነበረ ሲሆን፣የከተማዋ ውሃ እየተሟጠጠ ሄዶ በየቤታቸው የሚመጣውን ውሃ አጥተው ውሃ በራሽን ለማግኘት የሚሰለፉበት ሁኔታ ይመጣል የሚል ስጋት አድሮባቸው ቆይተዋል፡፡
ዘገባው እንዳመለከተው፣ ከድርቁ ጋር በተያያዘም ኬፕታውን ያለውሃ ልትቀር እንደምትችል እየተገመተ ይገኛል፡፡ የከተማዋ ባለስልጣናት ውሃ በቁጠባ በመጠቀም የከተማዋን የውሃ መጠን እንዲታደጉ ጥብቅ ትዕዛዝ ሲያስተላልፍ ቆይቷል ፡፡
ባለፈው ጥር ወር ባለስልጣናት የከተማዋ ነዋሪዎች የውሃ ፍጆታ 50 ሊትር በቀን እንዲሆን መመሪያ አውጥተዋል፡፡መመሪያው ገላን በመጠኑ ለመለቃለቅ ፣በመጸዳጃ ቤት አንድ ጊዜ ብቻ ውሃ በመልቀቅ አገልግሎት ለማግኘት እንዲሁም በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ በማሽን ልብስ ለማጠብ እንደሚያስችል ታምኖበት ሲሰራ ቆይቷል፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

Published in ዓለም አቀፍ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።