Items filtered by date: Friday, 02 February 2018

አዲስ አበባ፡- ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ለአገሪቱ ስፖርት ዘርፍ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማበርከት አቅዶ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡የአትሌቲክስና የብስክሌት ክለቦችን በማቋቋም ስራ መጀመሩንም ገለፀ፡፡
የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተካ አባዲ እንደገለፁት፣ በሕትመት ዘርፍ የ96 ዓመታት ልምድ ያለው ተቋሙ ለአገሪቱ ስፖርት አስተዋፅኦ ለማበርከት፣ የድርጅቱን ገፅታ ለመገንባትና ለወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር በማሰብ ክለቦቹን አቋቁሟል፡፡ እንደርሳቸው ገለፃ፣ ድርጅቱ የጀመረው ስራ ለሌሎች ተቋማት ምሳሌ በመሆን ለአገሪቱ የስፖርት ዘርፍ ማደግ የበኩሉን አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡
‹‹ድርጅቱ ካለው እድሜ አንፃር በስፖርቱ ዘርፍ የሚጠበቅበትን ስራ አልሰራም›› ያሉት ስራ አስፈፃሚው፣ በ2010 ዓ.ም አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በመመደብ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ በዚህም የአሰልጣኞችና የስፖርተ ኞች ቅጥርና ምልመላ መጠናቀቁን፣ ለክለቦች ልምምድና ውድድር የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች መሟላታቸውንና የደመወዝና ሌሎች አገል ግሎቶች እየተፈፀሙላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በኢትዮጵያ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማና ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝና በቀጣይም በእግር ኳስና በሌሎች ስፖርቶች ክለቦችን ለማቋቋም እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን አቶ ተካ አስታው ቀዋል፡፡
የአትሌቲክስ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ መላኩ ደረሰ በበኩሉ ፣ ስድስት ወንዶችንና ሁለት ሴቶችን በመመልመል ስራ መጀመሩንና በ2010 ዓ.ም በረጅም ርቀት አስር አትሌቶችን ለመምረጥ መታቀዱን ተናግሯል፡፡ አገሪቱ በአትሌቲክስ ዘርፍ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያስመዘገበችውን ውጤት ለማስቀጠል የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጣም ገልፀዋል፡፡
የብስክሌት ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ሮቤል ገብረማርያም እንዳስታወቀው የብስክሌት ክለቦች ቁጥራቸው እየበዛ ሲሄድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማ የሚሆኑ ፕሮፌሽናል ተወዳዳሪዎች ማፍራት ይቻላል፡፡ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የብስክሌት ቡድን ውጤታማ እንዲሆን ጥረት እንደሚያደርግም ተናግሯል፡፡
የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ሰራተኞች የስፖርት እንቅስቃሴ የረጅም ጊዜ ታሪክ እንዳለው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

አንተነህ ቸሬ

Published in ስፖርት

ከሦስት ሺ ዓመት በፊት በህንድ አገር እንደተጀመረ የሚነገርለት የውሹ ስፖርት ወደ ቻይና ተወስዶ የቻይና ባህላዊ ስፖርት ሆኖ ማደጉን የስፖርቱ ታሪክ ያስረዳል፡፡ ውሹ የሁሉም ስፖርቶች አባት መሆኑና ቴኳንዶን ጨምሮ ሌሎች የማርሻል አርት ስፖርቶች ከውሹ የወጡ መሆናቸው ይነገራል፡፡ ባህላዊና ዘመናዊ በመባል የሚከፈለው ውሹ ስፖርት በርካታ የጥበብ ዓይነቶች ያሉት ሲሆን፤ ዕድሜ የማይገድበውና በማንኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ ያለ ሰው ሊሰራቸው የሚችሉ የስፖርት ጥበቦች የያዘም ነው፡፡
በባህላዊ የውሹ ስፖርት ለቁጥር የሚያዳግቱ ጥበቦች ያሉ ሲሆን፤ ዘመናዊ ውሹ በሚባሉ ብቻ 11 የውድድር ዓይነቶች ይገኛሉ፡፡ ታዋቂው የውሹ ስፖርት ማስተር ብሩስሊን እንደሚለው ውሹ የፍልሚያ ብቃት ሳይሆን አካልንና አዕምሮን በማቀናጀት አንድ ድርጊትን በፍጥነት ማከናወን የሚያስችል ስፖርት ነው፡፡ ይህም ውሹ እባብና ነብርን ጨምሮ በርካታ እንስሳትን በመጠቀም የአካል ፍጥነትን ከአዕምሮ ፍጥነት ጋር በማቀናጀት አካልን ከአዕምሮ እኩል የማዘዝ ክህሎት ስለሚጠይቅ ስፖርቱ ፈታኝና ከባድ እንዲሆን ማድረጉንም የዘርፉ ሰዎች ይናገራሉ፡፡
የውሹ አርት ስፖርትን በኢትዮጵያ ለማስፋፋትና ለማሳደግ ላለፉት 25 ዓመታት ሲሰራ የቆየው ድራገን-ሊ የውሹ ስፖርት ክለብ ሰሞኑን የተመሰረተበትን 25ኛ ዓመት የብር እዮቤልዩ በዓል በተለያዩ ደረጃዎች ያሰለጠናቸውን 89 ተማሪዎች በቢጫ፣ አረንጓዴ፣ ጥቁርና በተለያዩ ማዕረጎች በአራት ኪሎ ትምህርትና ስልጠና ማዕከል ባስመረቀበት ወቅት አክብሯል፡፡
የውሹ ስፖርት ክለቡ በእስካሁኑ ጉዞው 17 ሺ የውሹ ስፖርት ተማሪዎችን አሰልጥኖ ያስመረቀ ሲሆን፤ በርካቶችም በአዲስ አበባና በመላ አገሪቱ በአሰልጣኝነት እያገለገሉ እንደሚገኙ የክለቡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡አቅም የሌላቸው ንና የስፖርቱ ፍቅር ያላቸውን ወጣቶች በነጻ በማሰልጠን ለውሹ ስፖርት ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ያለ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ በዓመት ሁለት ጊዜ በሚካሄደው የከተማዋ ሻምፒዮና እንዲሁም በዓመት አንድ ጊዜ በሚካሄደው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና በርካታ ውጤቶችን በማስመዝገብ ስኬታማ የዘርፉ ስፖርተኞችን በማፍራት ላይም ይገኛል፡፡ ክለቡ ባለፈው 2009ዓ.ም በተካሄደው የውሹ ስፖርት ውድድር ብቻ ዘጠኝ ዋንጫዎችን ማንሳት እስካሁን በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የ147 ዋንጫዎች ባለቤት መሆን የቻለ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ውሹ ፌዴሬሽን ቴክኒክ አማካሪና የድራገን-ሊ የውሹ ስፖርት ክለብ መስራችና አሰልጣኝ ማስተር አህመድ አብደልቃድር እንደሚሉት፤ ክለቡ የተመሰረተው ከ25 ዓመት በፊት ቢሆንም በወቅቱ በነበረው መንግሥት ማርሻል አርት ስፖርትን ማዘውተር አይፈቀድም ነበር፡፡ ይህም ክለቡን በወቅቱ የሚጠበቅበትን እንዳይሰራ አድርጓል፡፡ ሆኖም ባለፉት 25 ዓመታት ህጋዊ እውቅና በማግኘቱ ለውሹ ስፖርት ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ ችሏል፡፡
ድራገን-ሊ ውሹ ስፖርት ክለብ በ1984 ዓ.ም እንደተቋቋመና ስፖርቱም በመንግሥት ደረጃ ይሁንታ አግኝቶ ማርሻል አርት በስፖርት ደረጃ መዘውተር እንደተጀመረ የሚናገሩት ማስተር አህመድ፤ ባለፉት 25 ዓመታት ስፖርቱን በኢትዮጵያ በማሳደግ፣ አገሪቱ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲኖራት በማድረግና በዘርፉም ዋንጫ በማምጣት ክለቡ ውጤታማ ሥራዎችን መስራት ችሏል፡፡
በተለይ ማርሻል አርት ስፖርቱ አንድን ሰው ከማንኛውም ሱስ እንዲርቅ፣ ጊዜውን በአግባቡ እንዲጠቀም፣ ለሥራ ተነሳሽና ቀልጣፋ እንዲሆን ስለሚያደርግ በማህበራዊ ህይወቱ የተመሰገነ፣ ከሰዎች ጋር ያለው ግንኙነት ጤናማ የሆነና ቤተሰባዊ ህይወቱ የሰመረ እንዲሆን በማስቻሉ «በግሌ የተሳካ ህይወት እያሳለፍኩ እገኛለሁም» በማለትም ማስተር አህመድ ይናገራሉ፡፡
ማስተር አህመድ እንደሚሉት፤ ስፖርቱ ጤናማና አምራች ዜጋ ከመፍጠር ባሻገር ሰብዕና ያለው፣ በራሱ የሚተማመን፣ ለታናሹ የሚያዝን፣ ታላቁን የሚያቀርብ አገር ወዳድ እንዲሁም ምክንያታዊ የሆነ ዜጋ ለማፍራትም ያስችላል፡፡ ባለፉት ጊዜያት ከፓይለትነትና ዶክተርነት ጀምሮ የሁለት ሙያ ባለቤት የሆኑ ዜጎች በክለቡ የተፈጠሩ ሲሆን፤ ይህም ክለቡ ስኬታማና ንቁ ዜጋ ለማምረት አልሞ የተነሳውን ህልም እያሳካ ለመሆኑ ማሳያ በመሆናቸው መስራቹን ወደ ተሻለ ውጤት የሚያነሳሳ ነው፡፡ ማህበራዊ እሴትን ለማጎልበትም ከፍተኛ ፋይዳ አለው፡፡
ዓለም አቀፍ ውድድሮች በብዛት አለመኖ ራቸው የክለቡንና ክለቡ የሚያሰለጥናቸውን ስፖርተኞች አቅም በዓለም አቀፍ መድረክ ማሳየት እንዲሁም የአገር ገጽታን መገንባት አለመቻሉን የሚገልጹት አሰልጣኙ፤ አንድ አሰልጣኝ ብቻውን በሚያደርገው ጥረት ብቻ ስፖርቱን ማሳደግና የአገሪቱን ስም ማስጠራት ስለማይቻል የመንግሥት አካላት ውሹ ስፖርትን ሊደግፉት ይገባል፡፡ በተለይም ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የዘርፉ ስፖርተኞች የሚወዳደሩበትን መድረክ ማጎልበት እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡
«ውሹ ከሦስት ሺ ዓመት በፊት የተጀመረና የሁሉም ዓይነት ስፖርቶች መነሻ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ባሉ ትውልዶች ሲሰላ አሁን ላይ 33 ወጣት ትውልዶች እየሰሩት የሚገኝ ስፖርት ጥበብ ነው፡፡ በአገር ደረጃ ያለው እንቅስቃሴም በፊት ከነበረው አበረታች ቢሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ግን ብዙ መሰራት አለበት፡፡» ያሉት ማስተር አህመድ፤ ስፖርቱ እንደ ሌሎች አትሌቲክስ፣ እግር ኳስና መሰል ስፖርቶች ትኩረት ቢሰጠውና ሙያተኛው ድጋፍ ቢደረግለት አገሪቱን በውሹ ስፖርት ማስጠራትና ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንድታገኝ ማድረግ ይቻላል ባይ ናቸው፡፡ ለአብነት እ.አ.አ በ2002 በ«አፍሪካ አፍሮ እስያ ሻምፒዮን» ላይ የኢትዮጵያ አሰልጣኞች ሁለት ዋንጫ ማምጣት መቻላቸውንና እርሳቸውም ባለፈው ህዳር 20 እስከ 25 በተካሄደው ሰባተኛው ዓለም አቀፍ ሻምፒዮን ላይ አራት ዋንጫ ይዘው መምጣታቸውን ያነሳሉ፡፡
ማርሻል አርት ለፊልም ኢንዱስትሪው የሚሰጠው ግብዓት ቀላል አለመሆኑንና በወጣቱ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ከፍተኛ መሆኑ ድጋፍ ቢደረግለት በዓለም ደረጃ ስመጥር ሙያተኞችን ማፍራት እንደሚቻልም የሚናገሩት ማስተር አህመድ፤ ቻይናውያን ስፖርቱን በማሳደጋቸውና ሁሉም ዜጋ ከህጻንነት ጀምሮ እንዲሰራው ማድረጋቸው የትም ቦታ ተንቀሳቅሶ መስራት የሚችል ጠንካራና ሥራ ወዳድ ማህበረሰብ መፍጠር መቻላ ቸውንም ያብራራሉ፡፡
ስፖርቱን በአገሪቱ ለማስፋፋት ባለፉት 25 ዓመታት በተደረጉ ጥረቶች ስኬቶች ቢመዘገቡም በቂ የማዘውተሪያ ቦታ አለመኖርና ስልጠናው እየተሰጠ ያለው በወጣቶች ማዕከልና በቀበሌ አዳራሾች መሆን በተፈለገ ወቅት ሰዓት ከፋፍሎ ወጣቶችን ለማስተማር እንቅፋት ፈጥሯል፡፡ ይህም ዘርፉን በይበልጥ ለማሳደግ ተግዳሮት ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ ችግሩ እስካሁን መፍትሄ ባለማግኘቱ በዘርፉ ዕድገት ላይ ተግዳሮት ሆኖ ቀጥሏል በማለትም ማስተር አህመድ አስረድተ ዋል፡፡
በቀበሌ ውስጥ ያሉ አዳራሾች ቢፈቀዱም ለተለያየ አገልግሎት ስለሚውሉ በቁሳቁስ በማደራጀት ለስፖርቱ ምቹ በሆነ መልኩ ማስተካከል አይቻልም፡፡ ይህም የስፖርቱ ፍላጎት ያላቸውን ወጣቶች ለመሳብ ችግር ፈጥሯል፡፡ እንዲሁም ማህበረሰቡ ማርሻል አርት ስፖርትን እንደ ድብድብ መቁጠሩና ስፖርቱ ያለውን ፋይዳ መረዳት አለመቻሉ በዘርፉ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አስከትሏልም፡፡ ከዚህ አኳያ በፌዴሬሽኑ የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራዎች በስፋት መሰራት አለባቸው ይላሉ፡፡
«በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው አስተሳሰብና የማርሻል አርት ስፖርት ሳይንስ የተለያዩ ናቸው፡፡ ቻይናን ብንወስድ ስፖርቱ ብቃት ያለው ዜጋ ለመፍጠር ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት ሁሉም ዜጋ ከልጅነቱ እንዲማረው በማድረጋቸው ስልጠናው ዛሬ ላይ ለደረሱበት የዕድገት ደረጃ ከፍተኛ ጠቀሜታ አስገኝቶላቸዋል፡፡ ስፖርቱን በደንብ ተግባራዊ ማድረጋቸው አገሪቱ በምትነድፋቸው ሥራዎች ሁሉ ህዝባቸው የሚፈልጉትን ዓይነት ሥራ ሳይሰላች እንዲሰራ አስችሎታል፡፡
«ይህም ለሥነ-ምግባራቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቶላቸዋል፡፡ ስፖርቱ በምድር ላይ የማይቻል ነገር እንደሌለ በንድፈ ሃሳብ አስተምሮ በተግባር ያረጋግጣል፡፡ ውጤት ማግኘት የሚቻለው በመስራት ብቻ እንደሆነና በአቋራጭ ተሂዶ ምንም ውጤት ማምጣት እንደማይቻል ያስተምራል፡፡ በእዚህ መጠቀም አልቻልንም፡፡ በተለይ የአሁኑ ትውልድ የሚያደክም ሥራ መሥራት አይፈልግም፤ ይህ ደግሞ ጠንካራ ዜጋ ለመፍጠር የሚደረገውን ጉዞ ያሰናክላል፡፡ ዕድገት ከተፈለገ የሚሰራና ጠንካራ ትውልድ ማፍራት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ማርሻል አርት ውሹ መሰረት ነው፡፡» በማለትም ማስተር አህመድ ይጠቁማሉ፡፡
ማስተር አህመድ ማርሻል አርት ስፖርት በግል ደረጃ ጤናማ ኑሮ እንዲኖሩና ጥሩ ሰብዕና እንዲኖራቸው ያስቻለ መሆኑን፣ ይህን ማህበረሰቡ መረዳት እንዳለበትና መገናኛ ብዙሃንም የግንዛቤ ማሳደጉን ሥራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው፤ በተለይም በዘርፉ ያሉ ችግሮች በተግባር እንዲፈቱ በማድረግ መልካም ዜጋ ለመፍጠር የሚደረገውም ጉዞ ማገዝ እንዳለባቸው ይገልጻሉ፡፡ ሙያተኞችም በአዳራሾችና በማሰልጠኛ ማዕከላት ብቻ ታጥሮ መቀመጥ ሳይሆን ጉዳዩን ወደ ህዝብ በማውረድና መንግሥት ያለበትን ኃላፊነት እንዲወጣ በማድረግ መንቀሳቀስ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
እንደ ማስተር አህመድ ገለጻ፤ አሁን ላይ ያለው ትውልድ የስፖርት ጫና መስማት የማይፈልግና ጠንካራ አለመሆን ተወዳዳሪ የሚሆን ትውልድ እየጠፋ ነው፡፡ ከ10 እና 15 ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር እንኳ እየደከመ መጥቷል፡፡ ይህም አሰልጣኞች እንደ ወላጅም፣ አሰልጣኝም፣ ገሳጭም ሆነው እንዲሰሩ በማድረጉ በአሰልጣኞች ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል፤ ስጋትም ሆኗል፡፡ ለዚህም አንዱ ምክንያት የቤተሰብ እገዛ አነስተኛነት ሲሆን፤ ልጃቸው ህልመኛ ሆኖ በንቃት እንዲሰራ ለማድረግ ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡
እያንዳንዱን ቴክኒካል ስልት ተመልክቶ ልጆቹን ለመቀየር የሚደረገው ጉዞ ስፖርቱን አድካሚ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ሆኖም ከስፖርቱ አድካሚነት ጋር ሲነጻጸር የሚገኘው ገቢ እስካሁን አነስተኛ ነው፡፡ ይህም በርካታ አሰልጣኞች ስፖርቱን እየወደዱ ማሰልጠኑን እንዲያቋርጡና ወደማይፈልጉት ሥራ እንዲገቡ እያደረገ ነው የሚሉት ማስተሩ፤ በዘርፉ የሚደረጉ ውድድሮች ቢጠናከሩና እውቅና ቢሰጣቸው አሰልጣኞችን ለማበረታታት ጥሩ ነውም ባይ ናቸው፡፡
በአሁኑ ወቅት በተለይ በከተሞች ሺሻ ቤት፣ ጫት ቤት፣ መጠጥ ቤትና ተዛማጅ ሱሶች ተስፋፍተው በሚገኙበት ሁኔታ በአዕምሮ፣ አካልና ሥነ-ልቦና ጠንካራ የሆነ ልጅ ለመፍጠርና በአገር ደረጃ አምራችና ባለቤትነት የሚሰማው ቤተሰብ ለማፍራት ስፖርቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስላለው ወላጅ የልጁን ውሉ መከታተልና ማረም እንደሚገባውም ማስተር አህመድ ያሳስባሉ፡፡ አገሪቱን ሊረከባት የሚችል ከሱስ፣ ከሙስና እንዲሁም ከመጥፎ አመለካከት የጸዳ ወጣት በመሆኑ ብዙ መሰራት እንዳለበትና መንግሥትም እየተዳከሙ ያሉትን ስፖርት ቤቶች በማጠናከርና በማገዝ አምራች ዜጋ ለማፍራት የሚያደርገውን ጉዞ ስኬታማ ማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
በድራገን-ሊ ውሹ ስፖርት ክለብ ለስምንት ዓመታት በመሰልጠን «ፈርስት ዳን» ሆኖ የተመረቀው ፈርስት ዳን አሉላ አለማየሁ እንደሚናገረው፤ ውሹ ስፖርት በዋናነት የሚያስተምረው ማንኛውንም ነገር ማድረግ እንደሚቻልና ሞክሬ አልተሳካልኝም የሚለውን የተሳሳተ አስተሳሰብ በመተው ደጋግሞ በመሞከር ማሳካት እንደሚቻል በተግባር የሚያረጋግጥ ስፖርት ነው፡፡
ዳን አሉላ እንደሚለው፤ ስፖርት ሲጀመር አሰልችና አድካሚ ቢሆንም በውስጡ የሚገኙ በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት በመሆኑና በሂደት ለውጣቸውን ማየት ስለሚቻል ጠንክሮ መስራት የሚያስገኘውን ፋይዳ ያስተምራል፡፡ ውሹ ስፖርት ደግሞ ከሰዎች ጋር በቀላሉ ለመግባባት፣ ምክንያታዊ ለመሆን፣ በራስ ለመተማመን፣ ስህተት እንኳ ቢኖር ከስህተት ለመማርና የማይታወቅ ነገር ካለ በመስራት ማወቅ እንደሚቻል ያስተምራል፡፡
«በተለም የማትግባባበት ነገር ቢኖር በድርቅና ሳይሆን በመነጋገር መግባባት እንድትችል፣ የተሻለ እውቀት ቢኖርህ እንኳ የማታውቀው ነገር ሊኖር እንደሚችል በመረዳት ሌሎችን እንድታደምጥ፣ ለራስህ ፖሊስ እንድትሆንና ከሚሰነዘርብህ ጥቃት መከላከል እንድትችል፣ በሰው ላይ እንዳትደርስ፤ ከደረሱብህ መብትህን እንድታስከብር ያደርግሃል» ያለው ፈርስት ዳን አሉላ፤ አካልህ ከአዕምሮህ ጋር እኩል በማዘዝ ንቁ፣ አስተዋይና ሩቅ አሳቢ እንድትሆን ይረዳል ነው ያለው፡፡
«በድራገን-ሊ ውሹ ስፖርት ክለብ ጠንካራ መሆን እንደሚቻልና በአቋራጭ የሚገኝ ነገር አለመኖሩን፤ ቢገኝም ዘላቂ እንደማይሆን መማር ችያለሁ፡፡ ደክመህና ለፍተህ እንድታገኝ ያደርግሃል፡፡ በርካታ አሰልጣኞች ከዚህ ክለብ የወጡ ሲሆን፤ ለዘርፉ ዕድገትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለ ማዕከል ነው፡፡» በማለትም ፈርስት ዳን አሉላ ተናግሯል፡፡
በአሁኑ ወቅት ምክንያታዊነት እየጠፋ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በአገር ዕድገት ላይ ብቻ ሳይሆን በህዝብ ሰላም ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ እያስከተለ ነው፡፡ ስፖርት ቤቶች ተገቢ ድጋፍ አለማግኘታቸውና የወጣቱ ሰብዕና በስፖርት የተቀረጸ አለመሆን፣ መስራት ከተቻለ ከተባለው ቦታ መድረስ እንደሚቻል አለማመንና ተስፋቢስነት እየተስፋፋ ከመምጣቱ ጋርም ይያያዛል፡፡ በመሆኑም ስፖርት ቤቶችን ማጠናከርና ወጣቱ ከትምህርቱ ጎን ለጎን አካሉንና አዕምሮውን ሊያዳብሩለት በሚችሉ ዘርፎች ላይ መሳተፍ አለበት በማለትም ፈርስት ዳን አሉላ ይናገራል፡፡
ስፖርቱ በርካታ መሳሪያዎችን የሚጠቀም ሲሆን፤ ዘመናዊ ውሹ ከሚባሉት መካከል ቀጭኔ (ስፒር)፣ ከጀል፣ ሎንግሶዋርድ፣ ብሮሶዋርድ፣ ታይቺ፣ ታይጂጂያን፣ ናንዳው፣ ናንገን፣ ሳንሹ (ሦስቱንም የማጥቂያ ስልቶች ቦክስ፣ እግርና ትግል የያዘ ነጻ ፍልሚያ) ይጠቀሳሉ፡፡

ዑመር እንድሪስ

Published in ስፖርት

በመኖሪያ ከተማዬ የመጀመሪያውን ባለ ሁለት ወለል መኪና ዛሬ ተሳፈርኩበት፡፡ ይህ መኪና አገራዊ ብሎም አህጉራዊ ፋይዳው ቀላል አይምሰላችሁ። በተለይ በአፍሪካ ቀንድ ክፍለ አህጉር የተረጋጋ የትራንስፖርት ሰላም እንዲሰፍን ይህ ተሽከርካሪ የማይናቅ ሚና አለው፡፡ ረጃጅም የሆነውን ሰልፍ በመቀነስም ሆነ፤ በርከት ያሉ ሰዎችን በመያዝ የማይተካ ነው ብል ማጋነን ላይሆን ይችላል፡፡ በከተማዋ ነዋሪዎች አጠራር «አስር ዘጠና ወይም አርባ ስልሳው» የከተማ የትራንስፖርት አውቶቡስ፡፡
ብዙ ጊዜ የታሪካችንን ትሩፋቶች አመጣጥ ስንገልጽ ‹‹ ሲወርድ ሲዋረድ›› የመጣ እንላለን ምን ማለታችን ነው? ‹‹ሲወርድ›› የሚለውስ ይሁን ‹‹ሲዋረድ›› ማለት ምን ማለት ነው? ለማንኛውም ቃሉ ሲወርድ ሲወራረድ ነው፡፡ እናም ሲወርድ ሲወራረድ የኖረው አንበሳ የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት መልኩን ቀይሮ ባለ አንድ ፎቅ ማለቴ ባለ አንድ ቆጥ የሚል ስያሜን አንግቦ የተሳፋሪውን የትራንስፖርት እጥረት ለማቅለል በአዲስ መልክ ብቅ ካለ ሰነባብቷል፡፡
አዲስ አበባችን ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ መኪና እየተስተዋለባት ነው፡፡ ከባለ ሁለት እግር ጀምሮ እስከ ባለ ስምንት እግር ተሽከርካሪዎች ከተማዋ ላይ ሽር ጉድ ሲሉ ላያቸው ሰው የብዙ መኪናዎች ህብረ ብሄራዊነት ይመስላል፡፡ ምክንያቱም አዲስ አበባ የብዙ ብሄር ብሄረሰቦች መቀመጫ ብቻም ሳትሆን የብዙ መኪናዎች መናኸሪያም ጭምር እየሆነች ነው፡፡ በየጊዜው ከጥቃቅንና አነስተኛ መኪናዎች እስከ መካከለኛና ከፍተኛ መኪናዎች ዓይናችን ሳይታክት፣ ልባችን ከምኞት ሳይዘል በየዓይነቱ እንኮመኩማለን፡፡ የምናያቸው መኪናዎች የሚይዟ ቸውንም ሰዎች ጭምር እንድንለይ የሚያደርጉ ናቸው፡፡
እግረኛውም ተሽከርካሪውም እኩል የሚታዩበት መዲናችን በቅርቡ ለህዝብ አገልግሎት ካዋላቻቸው ተሽከርካሪዎች መካከል በሆቴልኛ ባለ አንድ ኮኮብ፣ በጋራ መኖሪያ ቤት አጠራር ደግሞ የተሽከርካሪው ቁጥር ጥቂት በመሆኑና ፍጥነት ስለሌለው አርባ ስልሳ የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲሱ አንበሳ የከተማ አውቶቡስ ብዙዎችን አነጋግሯል፡፡ ተንቀሳቃሽ ሕንፃ ሲሉም ይጠሩታል፡፡ በእርግጥ አውቶቡሱ ‹‹ከኮብል ስቶን›› ጠለል በላይ ከፍ ብሎ መታየቱ ብርቅ የሆነብን አገር ቤት ውስጥ ላለነው እንጂ በሌላው ሀገር ላይ በከፍታቸውም ይሁን በእርዝመታቸው አንቱታን ያተረፉ ከባለ አሽከርካሪ እስከ አሽከርካሪ አልባ መኪናዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡
መቼም አዲስ ነገር መፍጠር ይሳነን እንጂ ያለመድነው እንግዳ ክስተት የመጣብን ጊዜ አቀባበላችን ልዩ ነው፡፡ ለምን እንዲህ አልክ አትበሉኝ እንጂ ካላችሁኝ ግን ካልታዘባችሁኝ በስተቀር ትዝብቴን ላካፍላቹ፡፡ የሩቅ ክስተቶችን እንተወውና የቅርብ የቅርቡን ብንዳስስ እንኳን አንድ ለእናቱ የሆነው ባቡራችን ሥራ የጀመረ ጊዜ ህዝቡ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ለእናት አገር የክተት አዋጅ እንደተጠራ ሰራዊት ከያለበት አቅጣጫ እየተመመ መጥቶ ዳግማዊ ምኒልክ አደባባይና ቃሊቲ ላይ ሰፈሩ፡፡ በሄዱበት ባቡር እየተመለሱ በተመለሱበት እየሄዱ ሄደውም እየተመለሱ እየተመላለሱ… የባቡር ጉዞ ናፍቆታቸውን ለመበቀል ገንዘባቸውን መስዋዕት ያደረጉ የወንዜ ሰዎች ጥቂት አልነበሩም፡፡ ያው እኛ ጋር የጉልበት መስዋዕትነት ስለይማቆጠር ነው ያልጠቀስኩት እንጂ፤ ነገሩማ ጉልበትና ወገብን የሚያብረከርክ ረጅሙን የባቡር ሰልፍ ዘንግቼው አይደለም፡፡ ወዝና ቫዝሊን መቅኔ የሚያቀልጠውን የሸገርን ሚጥሚጣ የመሰለ የፀሐይ ሀሩር ታግሶ የባቡሩን መምጫ ሰዓት በጉጉት ለሚጠብቀው ለእኛ ሰው ግን ወጪ ማለት ገንዘብ እንጂ እንደ ጊዜና ጉልበት አይሰላም፡፡
መንግሥት በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት ከባቡሩ ያገኘውን ገቢ በመመልከት ምን ያህል የሥራ ፈት ህዝብ ቁጥር እንዳለ ያወቀው ያኔ ይመስለኛል፡፡ መቼም ሥራ ያለው ሰው ሙሉ ቀን በባቡር ሲመላለስ አይውልም ብዬ ነው፡፡ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭው ክፍል በመጀመሪያው ወር ካገኘው ገቢ አንፃር አጠቃላይ የዓመቱ ገቢ ሲሰላ ልዩነት እንብዛም ነው፡፡ ለምን ካሉ አሁን ለሥራ ከሚመላለሱት ደንበኞች አኳያ ሲሰላ ያለ ሥራ በወረት ከተመላለሰው ህዝብ ያገኘው ገቢ የላቀ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ እኔም ያኔ ነው ወረት ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ሊሆን እንደሚችል የገባኝ፡፡
አሁን ደግሞ ሰሞነኛው ባለ ቆጥ አንበሳ የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት አውቶቡስ ሥራ ሲጀምር መስሪያ ቤቱ ገቢው ከወትሮ ላቅ ያለ ይመስላል፡፡ ምክንቱም ይቺ ወረት ሥራዋን እየሠራች ነዋ፡፡ ደግሞም የወረተኛ ተገልጋይ ባህሪ ለአንበሳ አውቶቡስ ብርቁ አይደለም፡፡ ፅጌሬዳ የመሰለው ቢሾፍቱ ባስ በመጣ ጊዜ አያቶቼን ሲያመላልስበት በነበረው ብርቱ ጉልበት የእኔንም ትውልድ የሚያገለግለው ‹‹ዳፍ›› ዓይንህን ለአፈር ብለነው የነበርን ሰዎች ስንት ነን? አሁን ደግሞ ባለ ቆጡን አምጥተውልን ቀድሞ በመስኮተ ትእይንት (ቴሌቪዥን) ብቻ ያየነውን አውቶቡስ በገሀዱ አየነው፤ ዳሰስነው፤ ተሳፈርንበትም፡፡
ለወትሮ ባዶ አንበሳ አውቶቡስ አጠገቡ ቆሞ ነገር ግን ገና ባልመጣ፤ ቢመጣም ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቶ በሚመጣ ታክሲ ውስጥ የትርፍ ትርፍ ሆኖ ለመሄድ ባዶውን አውቶቡስ የሚያሳልፍ መንገደኛ እኔን ጨምሮ ሁላችንም እራሳችንን ብንቆጥር እልፍ ነን፡፡ አሁንስ? አሁንማ ባዶ ታክሲ አጠገቡ ቆሞ ነገር ግን ገና ባልመጣና ቢመጣም ከአፍ እስከ ገደፉ በሞላ ባለ ቆጥ አውቶቡስ ውስጥ ቆሞ ለመሄድ ባዶውን ታክሲ የሚያሳልፍ መንገደኛ እኔን ጨምሮ እራሳችንን እንቁጠር፡፡
ይህ እውቶቡስ ሥራውን ሲጀምር የተጠቃሚው ቁጥር መጨመሩ ወረት ብቻ ሳይሆን የህብረተሰቡንም ስነ ልቦና በግልጽ የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡ ወደ አውቶቡሱ ሲገባ ወንበር መያዝ የሚጀመረው ከላይኛው ክፍል ነው የሚል ግዴታ የተቀመጠ ይመስል ትኬት የሚቆርጠው መንገደኛ ሁሉ ቀድሞ የሚወጣው ወደ ላይኛው ክፍል ነው፡፡ ምክንያቱም እስከ ዛሬ መንገዱን ሙሉ ዝቅ ብሎ ስለተጓዘ ዛሬ የከፍታ ጉዞ ምን እንደሚመስል ማረጋገጥን የጓጓ ይመስላል፡፡ ከላይ ወጥተው በሚጓዙ መንገደኞች ፊት ላይ አንድም የደስታ አንድም የፍርሀት አንድም የጥርጣሬ ስሜት ይነበብባቸዋል፡፡ የተጓዡን ስነ ልቡና ሳጤነው ከፍ ባሉ ቁጥር ደስታ የሚሰማቸው ሰዎች ሁሌም የበላይ የሆኑ ስለሚመስላቸው የወጡበት ደረጃ መልሶ ቁልቁል እንደሚያወርዳቸው ስለሚዘነጉ ነው፡፡ የፌርማታ ጉዳይ እንጂ ተራውን እየጠበቀ ዕድሉ ሲደርሰው የሚወርድ የሚወጣ የለም፡፡ ሌሎቹ ፍርሐትና ጥርጣሬ የሚሰማቸው ሰዎች ከፍ ባሉ ቁጥር ሊወድቁ እንደሚችሉ ጥርጣሬ ይገባቸዋል፡፡ ከወደቁም የሚጠብቃቸውን ጉዳት ስለሚያውቁት ይፈራሉ፡፡
የአውቶቡስ ውስጥ ጉዞና የሰው ልጅ ኑሮ ብዙ ነገር ያመሳስላቸዋል፡፡ በአውቶቡስ ውስጥ ረጅም መንገድ እየተገፋህ እየተዘረፍክና እየተረገጥክ ትጓዛለህ፡፡ በተቃራኒው እየገፋህ እየዘረፍክ እና እየረገጥክም ትጓዛለህ፡፡ ወንበር ከያዝክም እስከመጨረሻው ለማንም ሳትለቅ ትጓዛለህ፡፡ የቀደሙት የላይኛውን ክፍል ከያዙት እታችኛው መደብ ላይ ለመቆም ትገደዳለህ ግን ሁሉም ሰው በዚያው አውቶቡስ ውስጥ እኩል መብት ያለው መንገደኛ ነው፡፡
የከተማ እውቶቡሱን ሳስበው ከከተማው ሕንፃ ግንባታ ጋር ይመሳሰልብኛል፡፡ ምክንያቱም አሁን አሁን አዲስ አበባችን ቀና ብሎ ሰማይን የሚያማትር ሕንፃ በሰፊው እየገነባች ነውና፡፡ አሳንሰር ባይኖረውም ልክ እንደ ሕንፃዎቹ መወጣጫ ደረጃ የተገጠመለት መኪናውም ይህንኑ አመል የተላበሰ ነው፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ የቦሌ አካባቢ ልጆች የተለየ የአኗኗር ዘይቤ ይኑራቸው አይኑራቸው አላውቀም ምክንያቱም ቦሌ ኖሬ አላውቅምና እናም አንዱ ወዳጄ ስለ እነርሱ ሲያዋራኝ ቦሌዎች እኮ በአውቶቡስ አይሄዱም አሉኝ፡፡ ስለቦሌዎች አስቀድሜ ስለማውቅ ለምን አላልኩትም፡፡ እርሱ ግን ነገሩን ቀጠለ ‹‹በአንድ ወቅት ላይ አንዲት የቦሌ ሰፈር ልጅ ምንም ዓይነት የትራንስፖርት አማራጭ ስታጣ አውቶቡስን ሳትወድ በግዷ ተሳፍራበት ወደ ቤቷ ትሄዳለች፡፡ ቤቷ እንደ ደረሰች አባቷ ምነው ልጄ ህዝብ ህዝብ ሸተትሽኝ አላት፡፡ እርሷም መልሳ በህዝብ መኪና መጥቼ ነው አለችው›› አለኝ፡፡ ተመልከቱ አንድ አገር ላይ አንድ ከተማ ውስጥ ሆነን ኑሯችን ግን ለየቅል ነው፡፡ ለዚያውም ልኬታ በሌለው የልዩነት ደረጃ፡፡ ይህ ከጥቂት ጊዜ በፊት የነበረ፤ በአውቶቡስ መጓዝ የደሃው ህብረተሰብ፣ በታክሲ መሄድ መካከለኛ ገቢ ያለው ህብረተሰብ፣ በግል መኪና መሄድ ደግሞ ሀብታም ለሆነው የተሰጠ አኗኗር አሊያም የአጓጓዝ ልማድ የነበረ ቢሆንም፤ ዛሬ የትራንስፖርት እጥረቱ ሁሉን አንድ አድርጎ ያለውም የሌለውም አውቶቡስን መርጦ ይጓዛል፡፡
እንደስሙ አንበሳ ሆኖ ብዙ አስርት ዓመታትን ከአዲስ አበቤዎች ጎን የቆመው አንጋፋ እና ባለውለታው አንበሳ የከተማ ትራንስፖርት አውቶቡስ በአዲስ መልክ ሲመጣ ካየሁትና ከተቀየሩብኝ ነገሮች ውስጥ አንዱ አውቶቡሱ ላይ የተለጠፈው አንበሳ ጎፈሩ ነጭ ሆኖ ነው፡፡ አንዱን ወዳጄን ስለዚህ ጉዳይ ስጠይቀው ‹‹አንበሳው አርጅቶ ይሆናል›› አለኝ፡፡ ከሆነም አንበሳው እንጂ አውቶቡሱ ግን ዛሬም ያለ እርጅናና ጡረታ ህዝብን እያገለገለ ነው፡፡

አዲሱ ገረመው

Published in መዝናኛ

ለመሆኑ ‹‹የቴክኖሎጂ ዘመን ነው›› በሚባለው በዚህ ወቅት ዘመኑ ባፈራው ቴክኖሎጂ ወይም አዳዲስ በሆኑ የፈጠራ ውጤቶች የምንጠቀመው ስንቶቻችን ነን? ብለን ብንጠይቅ አብዛኛው ዕድሉን አያገኝም፡፡ ቴክኖሎጂን በአቅራቢያ የማግኘቱም ዕድል ጠባብ በመሆኑ የመጠቀም ሃሳቡም አይኖርም፡፡ቢኖርም አምኖ የሚቀበለው ጥቂት ነው፡፡ በሀገራችን እንደ ወጣት ብዙነህ መርጋ ያሉ ወጣቶች ግን የህብረተሰቡን ኑሮ የሚያቀሉ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን ከሠራው ወጣት ብዙነህ መርጋ ጋር በፈጠራ ሥራው ዙሪያ ቆይታ አድረገናል፡፡ ወጣት ብዙነህ ተወልዶ ያደገው በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቀራኒዮ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲሆን፣ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በእውቀት ወገኔ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በኮንፕሬሄንሲቭ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ነው የተማረው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም እንዳጠናቀቀ በጀነራል ዊንጌት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ አውቶሞቲቭ ኤሌክትሪክ ቴክኖሎጂ፣ ኤሌክትሪካል ኤሌክትሮኒክስ ቴክኖሎጂና ፊኒሺንግ ዲዛይን በተባሉ የትምህርት ክፍሎች ውስጥ በመማር የኤሌክትሪክ ሲስተም ዲዛይነር ሙያ ባለቤት ለመሆን ችሏል፡፡
ወጣቱ ወደ ፈጠራ የገባበትንም አጋጣሚ እንደገለጸው፣ ከሰባት ዓመት ዕድሜው ጀምሮ መጫወቻዎቹን በመፈታታት የተለያዩ ሙከራ ዎችን ያደርግ ነበር፡፡ ሙከራዎቹ ውጤታማ ስለነበሩና ወላጅ እናቱ ስላበረታቱት አዲስ ነገር የመፍጠር ፍላጎቱ እያደገ መጣ፡፡ የልጅነት ሙከራው በይበልጥ የዳበረው ጀነራል ዊንጌት ቴክኒክና ሙያ ትምህርትቤት ከገባ በኋላ ነው፡፡ ድረ-ገፆችን በመጠቀምና በቴክኖሎጂ ዙሪያ የተለያዩ መረጃዎችን በማንበብ የእውቀት አድማሱን በማስፋት በትምህርት ቤት ቆይታው ብዛት ያላቸው የፈጠራ ሥራዎች ለመሥራት በቅቷል፡፡ በሥራዎቹም የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡ ነፃ የውጭ የትምህርት ዕድልም አግኝቷል፡፡ ወጣት ብዙነህ ከሠራቸው የፈጠራ ሥራዎች መካከልም የተወሰኑትን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
የማብሪያና ማጥፊያ መቆጣጠሪያ
ወጣት ብዙነህ መነሻ የሆነውን የፈጠራው ሥራውን ሲያስረዳ፣ የመጫወቻ መኪናውን በሪሞት ወይም በመቆጣጠሪያ በመጠቀም እየነዳ ይጫወትበት ነበር፡፡ መቆጣጠሪያውንና መኪና ውን በመፈታታት የእያንዳንዱን ዕቃ አገልግሎት ይለያል፡፡ ጥቅማቸውን ከለየ በኋላ ነበር ከመኪናው ውስጥ ያገኛቸውን ገመዶችና ሞተር ወይም ዲናሞ ለቤት ውስጥ አገልግሎት ከሚውል ማብሪያና ማጥፊያ ኤሌክትሪክ ጋር በማገናኘት በሠራው መቆጣጠሪያ መሣሪያ አማካኝነት የቤት ውስጥ መብራቶችን ለማጥፋትና ለማብራት ጥቅም ላይ ያዋለው፡፡ ገመዱን በማገናኘትና በማለያየት እንዲያጠፋና እንዲያበራ በሚያደርገው መቆጣጠሪያ ማጥፋት ሲፈለግ ገመዱ ይለያያል፡፡ ማብራት ሲፈለግ ደግሞ ከመዱ ይገናኛል፡፡ በትንሽ የተጀመረው ሙከራ በኋላ ላይ ተሻሽሎ ከፍ ወዳለ አገልግሎት አድጓል፡፡ የተሻሻለው መቆጣጠሪያ የተሠራው በቴሌቪዥን መቆጣጠሪያ ወይም ሪሞት ነው፡፡ እርሱ እንዳለው ማብሪያና ማጥፊያው ላይ ሪሲቨር ወይም የሚቀበል መሣሪያ፣ መቆጣጠሪያው ላይ ደግሞ ትራንስሚተር ወይም አስተላላፊ መሣሪያ ተገጥሞላቸዋል፡፡ የተገጠሙት መሣሪያዎች መብራቱ እንዲበራና እንዲጠፋ ትዕዛዝ የሚቀበሉ ናቸው፡፡በዚህ የመቆጣጠሪያ ዘዴ እስከ 25ሜትር ርቀት ድረስ ማብራትና ማጥፋት ይችላል፡፡ ብዛት ባላቸው ክፍሎች ውስጥ የሚገኙትን መብራቶች በአንዴ ወይም በተናጠል ማጥፋትም ማብራትም ይቻላል፡፡ መቆጣጠሪያውን በተመሳሳይ ቴሌቪዥን ለመክፈትም ለመዝጋትም መጠቀም ይቻላል፡፡ መቆጣጠሪያው በባትሪ ድንጋይ ስለሚሠራ የሌክትሪክ ፍጆታ አያሰጋም፡፡
ወጣት ብዙነህ በሠራው የፈጠራ ሥራ በቤቱ እየተጠቀመበት እንደሆነም ገልፆልናል፡፡ ሰዎች ቢጠቀሙበት ሊያገኙ የሚችሉትን ጥቅም ሲገልጽ ብዙ ክፍሎች ያሉት መኖሪያቤት ያላቸው ሰዎች አንድ ክፍል ሆነው የሌሎቹን ክፍሎች መብራት ማጥፋት ወይም ማብራት ቢፈልጉ ባሉበት ቦታ ሆነው በመቆጣጠሪያው በመጠቀም ድካማቸውን መቀነስ እንደሚችሉ ይናገራል፡፡ ‹‹የብዙ ሰው የመኝታ ክፍሎች ማብሪያና ማጥፊያ አንድ ቦታ ብቻ በመሆኑ አልጋቸውን መቀየር እንኳን ቢፈልጉ ለማብሪያና ማጥፊያ ሲሉ ከአንድ ቦታ አይነሱም፡፡ መቆጣጠሪያው እነደዚህ ያሉ ችግሮችን ይቀርፋል፡፡ ለአካል ጉዳተኞች ደግሞ የበለጠ ይጠቅማል፡፡ መቆጣጠሪያው በእጃቸው ካለ የሌላ ሰው ድጋፍ አያስፈልጋቸውም፡፡ ፈጠራው መኖሩ በራሱ ትልቅ ነገር ነው›› ይላል፡፡
የጓሮ አትክልት ውሃ ማጠጫ መሣሪያ
ከዛሬ ሰባት ዓመታት በፊት ስለሠራው የጓሮ ውሃ ማጠጫ መሣሪያ እንደገለጸልን መሣሪያው የውሃ ማጠራቀሚያ፣ መሣሪያውን የሚያንቀሳቅስ ባትሪ፣ በሰዓት እየተቆጣጠረ አትክልቶቹን እንዲያጠጣ የሚያስችል የሰዓት መቆጣጠሪያ፣ ውሃውን ለማጠጣት ደግሞ ማብሪያና ማጠፊያ፣ የውሃ መሣቢያ ወይም ፓምፕ ያለው ሲሆን፣ በእነዚህ ሁሉ የታገዘው መሣሪያ በማጠራቀሚያው ውስጥ ያለው ውሃ በስበት ኃይል እየተገፋ አትክልቶቹን ውሃ ያጠጣል፡፡ አትክልቶቹ በቀን ሁለት ጊዜ ጠዋትና ማታ ያለማንም አስታዋሽ ውሃ እንዲጠጡ ያስችላል፡፡ አውቶማቲክ ወይም በራሱ የሚሠራው ይህ መሣሪያ፣ ሰዓት ጠብቆ አትክልቶችን በጠብታም ሆነ በግፊት አትክልቱን በሚያስፈልገው መጠን ውሃ ያጠጣል፡፡ ከውሃ ማጠራቀሚያው ውስጥ ውሃ ሲያልቅ ምልክት በማሳየት ውሃ ማለቁን በማሳወቅ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ከውሃ ማጠጫው ጋር የመሬቱን እርጥበት የሚያመጣጥን መቆጣጠሪያ መሣሪያም አብሮ በመገጠሙ ውሃው መሬት መድረሱን ወይም እርጥበቱን ያረጋግጣል፡፡ የመሬቱን እርጥበት የሚያረጋገጠው መሣሪያም በመሬት ውስጥ እንደሚተከል ገልጿል፡፡
መሣሪያው ግቢ ለማስዋብ የሚተከሉ የተለያዩ አበባ እና እፅዋት እንዲሁም የጓሮ አትክልቶችን ለማጠጣት በጣም ጠቃሚ እንደሆነ የገለጸው ወጣት ብዙነህ፣ አትክልቶቹ ተመሳሳይ በሆነ ሰዓት ውሃ እንዲያገኙ ከማስቻሉ በተጨማሪ የሰውንም ድካም እንደሚቀንስ ተናግሯል፡፡ መሣሪያው በፀሐይ ብርሃን ኃይል እንዲሠራ በመደረጉ የኤሌክትሪክ ወጪንም ለመቀነስ እንደሚረዳ አስረድቷል፡፡ የተፈጥሮ ኃይልን በመጠቀም አካባቢን እንዲህ ማልማት እንደሚቻልም በተግባር ማሳየቱን ይገልጻል፡፡ የሠራው ሞዴል የአትክልት ማጠጫ መሣሪያ 27 ካሬ ሜትር ድረስ የሚያጠጣ ሲሆን፣ 15ሺህ ብር ወጪ አድርጎበታል፡፡ የመሣሪያውን መጠን በማሳደግም በማሳነስም መሥራት ይቻላል፡፡
ወጣት ብዙነህ የሠራው የአትክልት ውሃ ማጠጫ መሣሪያ ዊንጌት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በነበረበት ወቅት ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ጥቅም ላይ መዋሉን ያስታውሳል፡፡ ሆሎታ አካባቢም አንድ ዘመዱ ለጓሮ አትክልት እንደተ ጠቀመበትና ውጤታማ እንደሆነም ገልጿል፡፡ ለከተማ ግብርና ሥራም እንደሚያ ገልግል ከተሞክሮው ነግሮናል፡፡ መሣሪያው ጥቅም ላይ እንዲውል ፍላጎት ቢኖረውም በተለያየ ምክንያት ወደተጠቃሚው ለማድረስ አለመ ቻሉንና ወደፊት ግን እንደሚያስተዋውቅ ገልጿል፡፡
የወጣት ብዙነህን ሌሎች ሥራዎችና በሥራዎቹ ያገኛቸውን ሽልማቶች እንዲሁም ነፃ የትምህርት ዕድል በተመለከተና የወደፊት እቅዱን ደግሞ በሚቀጥለው ሳምንት እናቀርብላችኋለን፡፡

ለምለም መንግሥቱ 

Published in ማህበራዊ

ወጣት ለውጥ ፈላጊ፣ አዲስ ነገር ፈጣሪ፣ብሩህ ተስፋ ያለው፣ነገሮችን በድፍረት የሚሞክርና የማይሰለቸው እንደሆነ በተለያየ መንገድ እንዲህ ስለወጣቱ የገለጹ ሰዎች የወጣትነት እድሜ ለመልካም ነገር ከዋለ እራስን ብቻ ሳይሆን ሀገር ላይም ለውጥ ማስመዝገብ እንደሚቻል ያምናሉ፡፡
አፍላ ጉልበቱንና አዕምሮውን ላልተገባ ነገር ካዋለውም ጉዳቱ የከፋ እንደሚሆን ይገልጻሉ፡፡ ለዚህም ነው በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ወጣቱ አጀንዳ የሚሆነው፡፡ የወጣቱን ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት እያረጋገጡ መሄድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱም በወጣቱ ዙሪያ የሚሠሩ የተለያዩ አደረጃጀቶች ተዋቅረዋል፡፡ ኃላፊነት ከተሰ ጣቸው መካከልም የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አንዱ ነው፡፡
ተቋሙ ተደራሽነቱ እስከምን ድረስ እንደሆነ በሚኒስቴሩ የወጣቶች ንቅናቄና ተሳትፎ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ማቲያስ አሰፋ እንዲህ ያስረዳሉ፡፡ ሚኒስቴሩ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና በፖለቲካ ተሳትፎ ማጎልበት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል፡፡ በኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ዙሪያ ከሚሠሩት ሥራዎች ወጣቱ በተናጠልም ሆነ በጋራ ተደራጅቶ የራሱን የኢኮኖሚ አማራጭ እንዲፈጥር ማስቻል ነው፡፡ በመሆኑም ወጣቱ ክህሎት ኖሮት የራሱን ሥራ እንዲፈጥር፣የመስሪያ ቦታና ለሥራ መነሻ የሚሆነው የብድር አገልግሎት እንዲያገኝ፣ ሚኒስቴሩ ከአስፈፃሚ ተቋማት ጋር በመሆን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ አብሮ ይሠራል፡፡
በተጨማሪም ወጣቱ ጠባቂ እንዳይሆንና በራሱ እንዲተማመን የንቅናቄ መድረኮችን በማዘጋጀት ትምህርታዊ ቅስቀሳ ያደርጋል፡፡ በተሠሩት ሥራዎችም በኢኮኖሚው ዘርፍ ወደ መካከለኛ ደረጃ የተሸጋገሩ የጥቃቅንና አነስተኛ አንቀሳቃሾችን መፍጠር ተችሏል፡፡ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይም የነበረው የተዛባ አመለካከት ተቀይሯል፡፡ ሥራ የማይመርጥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ምሩቅ እየተበራከተ ነው፡፡
ወጣቱና ማህበራዊ ጉዳዮችንም በተመለከተ ሚኒስቴሩ በተመሳሳይ ከማህበራዊ አገልግሎት ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ወጣቱ ለባህል ወረራና ለደባል ሱስ ተጋላጭ እንዳይሆን በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም ጫት ቤትና ሺሻ ቤት እንዲሁም የጭፈራና የመጠጥ ቤቶች በትምህርት ተቋማት አካባቢዎች እንዳይከፈቱ ቀድሞ የነበሩትም እንዲነሱ ከትምህርት ተቋማትና ከንግድ ሚኒስቴር ጋር በጋራ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሚኒስቴሩ ለአደጋ አጋላጭ የሆኑ ድርጊቶች በትምህርት ቤቶች አካባቢዎች እንዳይፈፀሙ መሥራቱን እንዲህ ቢገልጽም እውነታው ግን እርሳቸው ያሉትን የሚያሳይ እንዳልሆነ አቶ ማቲያስ ለቀረበላቸው ጥያቄ በተሠራው ሥራ ሁሉም እኩል በሆነ ደረጃ አለመንቀሳቀሳቸውን ገልጸዋል፡፡
መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ቀድሞ ወደ ሥራ በመግባት በትምህርት ተቋሙ ዙሪያ የነበሩ የሱስ አገልግሎት መስጫዎች ከአካባቢው እንዲነሱ በማድረግ ለአብነት ተጠቃሽ መሆን ችሏል፡፡ ተሞክሮውን በማስፋት በሁሉም አካባቢ በተመሳሳይ ውጤት እስኪመዘገብ ተከታታይነት ያለው ሥራ ያስፈልጋል፡፡
ወጣቱ አዕምሮውን የሚያዝናናበት ወደ 2ሺ400 የወጣት ማበልፀጊያ ማዕከሎች ተገንብተዋል፡፡ ማዕከላቱ በስፋት ያሉት በከተሞች ሲሆን፣አብዛኛው ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው የሚገኙት፡፡ ይሄም የተመጣጠነ ባለመሆኑ ጥያቄ የሚያስነሳበት አጋጣሚ እንደሚኖር አቶ ማቲያስ ያምናሉ፡፡ የወጣቱን ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ለማጎልበት በሚሠሩት ሥራዎች ተግዳሮቶች መኖራቸውን ይገልጻሉ፡፡
አቶ ማቲያስ እንዳሉት፤ ወጣቱ በተለያየ አጋጣሚ ያየውን ፈጠራ መተግበር ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን ፍላጎቱን መሠረት ያደረገ ፈጣን ድጋፍ ባለማግኘቱ ተስፋ መቁረጥ ይስተዋልበታል፡፡ የፈለጉትን ማሟላት ባይቻልም የተለያዩ መንገዶችን በማሳየትና የሚቻለውንም በማመቻ ቸት በየተቋሙ የሚገኙ አመራሮች የሚጠበቀውን ያህል እየተሠሩ አይደለም፡፡ ከወጣት የሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር የተያያዘው ጉዳይ በአብዛኛው የመልካም አስተዳደር ችግር ነው፡፡ ወጣቱ ለሚያቀርባቸው የብድር፣የግብዓት አቅርቦት፣ የመስሪያ ቦታና የተለያዩ ጥያቄዎችን በወቅቱ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ማበሳጨት ይስተዋላል፡፡ እንዲህ ያለው ችግር በማህበራዊ አገልግሎቶች ላይም ተመሳሳይ ነው፡፡ የሥነተዋልዶ ጤና አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ፣በተለያዩ ምክንያቶች ከትምህርት ገበታ የራቁትን ወጣቶች ከጎልማሶች ጋር የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ የማስቻል ሁኔታ አነስተኛ ነው፡፡
የወጣቱ የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲጎለብት በተሠሩት ሥራዎች ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ላይኛው እርከን ወጣት አመራሮችን መፍጠር ቢቻልም የፖለቲካ ምህዳሩ ለወጣቱ አሁንም እንጭጭ ደረጃ ላይ እንደሆነ አቶ ማቲያስ ይናገራሉ፡፡ በከፍተኛ የአመራርነት ቦታ፣ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤትና በተለያዩ እርከኖች ላይ በመረጃ የተደገፈ ወጣት አመራር መኖሩ መረጋገጥ አለበት፡፡ «ነገ ሀገሪቷን የሚረከብ ወጣት ዛሬ የአመራርነት ሚናውን የሚወጣ ወጣት ሲኖር ነው» ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ሚኒስቴሩ በዚህ ረገድም የተለያዩ የወጣቶች ንቅናቄ መድረክ በማመቻቸት ጭምር የፖለቲካ ተሳታፊነቱ እንዲጎለብት እየሠራ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያዊ እሴቶችን በማጎልበት ረገድም ጤናማ የሆነ የትውልድ ቅብብሎሽ እንዲኖር፣የሀገር ፍቅርና ተቻችሎ አብሮ የመኖር እሴቶች እንዳይቀዛቅዙ፣ የቀድሞውና የአሁኑ ትውልድ የሚገናኙበትን መድረክ በማመቻቸት ሥራዎች ቢሠሩም ክፍተቶች መኖራቸውን አቶ ማቲያስ ይገልጻሉ፡፡
እንደ አቶ ማቲያስ ገለጻ፤ ሚኒስቴሩ በወጣቱ ዙሪያ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ቢያደርግም ወጣቱን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች የሚሠሩት ከሚኒስቴሩ ውጪ በሆኑ አስፈጻሚ ተቋማት ነው፡፡ የሥራ አፈፃፀሞችንም የሚከታተለው ተቋማቱ በሚልኩለት መረጃ መሠረት ነው፡፡ ውሳኔ ሰጭ ባለመሆኑ ክትትልና ድጋፍ የሚፈለገውን ያህል ውጤት ለማስመዝገብ አላስቻለውም፡፡ የበጀት እጥረት አለበት፡፡ መንግሥትም መዋቅራዊ አደረጃጀቶችን መፍጠር እንዳለበት በመጠቆም፤ ሚኒስቴሩም በተለያዩ መድረኮች ላይ ሃሳቡን ማቅረቡንም ገልጸዋል፡፡
ካለፈው ዓመት ጀምሮ በሥራ ላይ የዋለው የወጣቶች የልማትና የለውጥ ስትራቴጂ ክፍተቶችን እንደሚያቃልል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ ስትራቴጂውው እያንዳንዱ አስፈፃሚ የመንግሥት ተቋም የወጣቶችን ጉዳይ አካቶ የሚሠራበትና ተጠያቂ የሚሆንበት የአሠራር ሥርዓት ያለው ሲሆን፤ ተቋማቱ ስትራ ቴጂውን በመተግበር ሥልጣንና ኃላፊነታቸውን በመወጣት ችግሮችን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ይቻላል፡፡ አብዛኛውን ወጣት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በሰፊውና ተደራሽ ለማድረግም የአርብቶ አደር የልማትና የለውጥ ፓኬጅ ተቀርፆ በሥራ ላይ ውሏል፡፡
ሚኒስቴሩ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ከማጎልበት ጎን ለጎን የወጣቶችን የሰላም እሴቶች በማዳበር እንደሚሠራ የገለጹት አቶ ማቲያስ «ወጣቱ ከሁከትና ግርግር ትርፍ እንደማያገኝና ምክንያታዊ እንዲሆን ግንዛቤ በማዳበር የመቻቻል፣ የአብሮነትና የሰላም ጥቅምን በማሳየት ይሠራል» ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ሚኒስቴሩ በተለያዩ የወጣት አደረጃጀቶች ከብሄራዊ ክልሎች ከተወከሉ የወጣት አመራሮች ጋር እንደሚሠራም አመልክተዋል፡፡
የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርን የሚከታተለው የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እያከናወነ ስላለው ተግባርም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ እንዳስረዱት፤ የወጣቶች አደረጃጀት መለዋወጥ አንዱና ትልቁ ችግር ነው፡፡ የወጣቶች ጉዳይ ቀደም ሲል ከሴቶችና ሕፃናት ሚኒስቴር ጋር ነበር፡፡ አሁንም ከስፖርት ጋር ተያይዟል፡፡ እንዲህ ያለው አሠራር ወጣቱ ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ ተልዕኮ ለመወጣት አያስችልም፡፡ ወጥ የሆነ አደረጃጀት እንዲኖር ቋሚ ኮሚቴው ከሚኒስቴሩ ጋር መክሮበታል፡፡
የወጣቱን ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት በማረጋገጥ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበትና ቁልፍ ተግባሩ አድርጎ መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅበት ቋሚ ኮሚቴው በእቅድ ዝግጅትና አፈፃፀም ክትትል ወቅት ከሚኒስቴሩ ጋር እንደሚነጋገር የገለጹት ወይዘሮ አበባ፤ ቋሚ ኮሚቴው ዋና ተግባሩ ሚኒስቴሩን መከታተል፣ መቆጣጠርና መደገፍ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ሰብሳቢዋ እንዳሉት፤ አስፈፃሚ መስሪያቤቶች የወጣቶችን ጉዳይ አካተው እንዲሠሩ በአዋጅ ሥልጣንና ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ አዋጁን መሠረት አድርገው መተግበራቸውን ከእቅድ ጀምሮ አፈፃፀማቸውን በመስክ ምልከታ ጭምር ክትትል እንዲደረግ በምክርቤት ደረጃ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ በመሆኑም በምክርቤቱ 18 ያህል አስፈፃሚ መስሪያቤቶችን የሚከታተሉ የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች የወጣቶችን ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት በሚያረጋግጥ መልኩ አካቶ መሠራቱን ይከታተላሉ፡፡ የወጣቶችን ጉዳይ አንድ ተቋም ብቻ የሚወጣው ባለመሆኑ ሁሉም አስፈፃሚ መስሪያቤቶች በተደራጀና በተቀናጀ አሠራር እንዲንቀሳቀሱ ለማስቻል እንደ አንድ ስትራቴጂ መያዙንና ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑንም ወይዘሮ አበባ አስረድተዋል፡፡
ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ተግባርና ኃላፊነቱን ለመወጣት ያለበትን የመወሰን አቅም ውስንነት በተመለከተም ወይዘሮ አበባ እንዳስረዱት፤ ሚኒስቴሩ ካሉት ሁለት ተልዕኮዎች የወጣቶችን ጉዳይ ሁሉም አስፈፃሚ መስሪያቤቶች አጀንዳ እንዲያደርጉት ማስቻል አንዱ ተግባሩ ሲሆን፣ ባለፉት ዓመታት ያልነበረ በዘንድሮ ዓመት የተሰጠው ትልቅ ኃላፊነት በሁለተኛ ደረጃ ይገለጻል። ይሄውም በ2008ዓ.ም የአስፈፃሚ አካላት ወይም መስሪያቤቶችን ተግባርና ኃላፊነት ለመወሰን በወጣው አዋጅ ላይ እያንዳንዱ አስፈፃሚ መስሪያቤት የወጣቶችን ጉዳይ አካቶ መሥራት እንዳለበት በህግ ማዕቀፍ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ በዚህ መሰረት ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የትምህርት፣የጤና የግብርና እና ሌሎችም አስፈፃሚ ተቋማት ወጣቶችን ማዕከል ያደረገ ሥራ ምን ያህል እንደሠሩ የመከታተል ተግባሩን እንዲወጣ አዋጁ ትልቅ አቅም ፈጥሮለታል፡፡ በመሆኑም ሚኒስቴሩ ኃላፊነቱን ምን ያህል ተጠቅሞበታል? የሚል በራሱ ላይ ጥያቄ እንደሚያስነሳበት ወይዘሮ አበባ አስረድተዋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያቤቶቹ ውስጥ ፎረም በማቋቋም ሥራዎችን መከታተል የሚቻልበትን አሠራር በመዘርጋት አሠራሩን ማቃለል እንደሚቻልም ወይዘሮ አበባ ይገልጻሉ፡፡ የማስፈፀም ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የትኩረት ጉዳይ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ለምለም መንግሥቱ  

Published in ፖለቲካ

ኢትዮጵያ ለዘመናት ከተለያዩ የውጭ ኃይሎች ጥቃት ሲሰነዘርባት በሕዝቦቿ ፅናት በየጊዜው የተነሱባትን ጠላቶቿን ድባቅ በመምታት ነፃነቷን አስጠብቃ የኖረች አገር ናት፡፡ የሕዝቧ ሰላም ወዳድነት ሰላምና መረጋጋት በራቀው የአፍሪካ ቀንድ (Horn of Africa) አካባቢ ሰላም ያላት አገር ሆና እንድትገኝ አስችሏታል፡፡ ይህም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተምሳሌት ሆና እንድትታይም አድርጓታል፡፡
አገሪቱ በየጊዜው ሉዓላዊነቷን ለመፈታተን የሞከሩ የውጭ ወራሪዎችን ድል በማድረግ ነፃነቷን ጠብቃ መቆየት ብትችልም የውስጥ ሰላሟ አስተማማኝ ስላልነበር አገሪቱ ፊቷን ወደ ልማት ለማዞር ተቸግራ ቆይታለች፡፡ ይህም አገሪቱና ዜጎቿ ድህነት መገለጫቸው እንዲሆን ምክንያት ሆኗል፡፡ በእርግጥ የአገሪቱ የውስጥ ሰላም በተለያዩ ወቅቶች የተለያየ ገፅታ እንደነበረው የታወቀ ቢሆንም በወታደራዊው የደርግ የአስተዳደር ወቅት የነበረው የአገሪቱ ሰላም ግን ለአገሪቱ ሕልውናም አስፈሪ እንደነበር መዛግብትና የዓይን እማኞች ያስረዳሉ፡፡
የደርግ ስርዓት በኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ከተገረሰሰ ወዲህ ባሉት ዓመታት የተገኘውና በአገሪቱ የሰፈነው ሰላም ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን አስገኝቷል፡፡ ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ ከማድረግ ጀምሮ አገሪቱ ትኩረቷን ወደ ልማት በማድረጓ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እንድታ ስመዘግብ አስችሏል፡፡
በኢትዮጵያ የሰፈነው ሰላም አገሪቱ በተከታታይ ዓመታት ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እንድታስመዘግብ ዋስትና ሆኗታል፡፡ አገሪቱ በብዙ መስኮች ያሳየችው እመርታም ከዓለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀር ምስክርነት ተችሮታል፡፡
የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፈጣን እድገት እያሳየ እንደቆየና እድገቱ ቀጣይነት እንደሚኖረው በተደጋጋሚ ገልጿል፡፡ ለአብነት ያህል ባንኩ በ2015 እ.አ.አ ባወጣው ሪፖርት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በአማካይ ከ10 በመቶ በላይ እድገት ማስመዝገቡን ይጠቅሳል፡፡
ባንኩ እ.አ.አ በህዳር 2015 ‹‹A Unique Economic Strategy Delivering High Growth›› በሚል ርዕስ ያወጣው ሪፖርት፣ የሀገሪቱ የዕድገት ግስጋሴ በዚሁ ከቀጠለ በ2025 እኤአ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ዝርዝር ልትቀላቀል እንደምትችል ይጠቁማል፡፡
በሌላ በኩል ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (International Monetary Fund - IMF) በበኩሉ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ፈጣን ዕድገት ማስመዝገቡን እንደሚቀጥል በቅርቡ ይፋ አድርጓል፡፡ የተቋሙ የአፍሪካ ጉዳዮች መሪ ጁሊዮ ኤስኮላኖ በኢትዮጵያ ባደረጉት የሥራ ጉብኝት፣ ተቋሙ ባደረገው ግምገማ መሠረት ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፈጣን ዕድገት ማስመዝገቡን ገልጸው፣ ኢኮኖሚው በሚቀጥለው ዓመትም ፈጣን ዕድገት የሚያስመዘግብ መሆኑን ገለጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ተቋሙ በሚያዝያ 2017 እኤአ ባወጣው ሪፖርት፣ በዚሁ ዓመት ሀገሪቱ በምሥራቅ አፍሪካ በአጠቃላይ ሀገራዊ የምርት መጠን ንግሥናውን ከጎረቤት ኬንያ መረከቧን አስታውቋል፡፡
ይህንን እውነታ ሌሎች አካላትም የሚጋሩት ሲሆን፣ ‹‹THE AFRICA REPORT›› የተባለው መጽሔት በ2014 ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም (International Monetary Fund – IMF)ን ዋቢ አድርጎ ባሰፈረው ጽሑፍ፣ ኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገቧንና የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገትም ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑን አትቷል፡፡ በተመሳሳይ የአፍሪካ ልማት ባንክ (African Development Bank - AfDB) በ2015 ሪፖርቱ የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ የሰፈነውን ሰላም በመጠቀም ግልጽ ሀገራዊ የዕድገት ራዕይ በመንደፍና ድህነት ተኮር የበጀት አመዳደብ በመከተሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከድህነት መላቀቃቸውን ጠቅሷል፡፡
በአገሪቱ የሰፈነው ሰላም ግዙፍ አቅም ያላቸውን የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብም አስችሏል፡፡ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ከሰላም መስፈን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስላላቸው ሀገሪቱና ሕዝቦቿ በፈጠሩት የተረጋጋ ሰላም ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ በስፋት ተሳትፈዋል፡፡
የዓለም ባንክ የ2016 እ.አ.አ የኢኮኖሚ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ በኢትዮጵያ የተመዘገበው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እ.አ.አ በ2005 ከነበረው 265 ሚሊዮን ዶላር በ2015 በአስር እጥፍ አድጎ 2.16 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ በ2008 ዓ.ም የበጀት ዓመት ደግሞ ይህ አሃዝ ሦስት ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ ያሳያል፡፡ በዚህም የምሥራቅ አፍሪካን ኢኮኖሚ በበላይነት ትመራው የነበረችውን ኬንያን በመብለጥ የክፍለ አህጉሩ የኢኮኖሚ ቁንጮ ለመሆን በቅታለች፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ እምርታ የተመዘገበው በአገሪቱ በሰፈነው ሰላም ምክንያት ነው፡፡
የውስጥ ሰላሟን በማጠናከር ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ በመሆን ስኬታማ ጉዞ ላይ የምትገኘው የምሥራቅ አፍሪካዋ ኢትዮጵያ፣ ግዙፍ መዋዕለ ንዋይ የሚያንቀሳቅሱ የውጭ ባለሀብቶችን በመሳብና ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የሥራ ዕድል በመፍጠር በዘርፉ የአፍሪካ መሪ ለመሆን እየተንደረደረች እንደምትገኝ ኧርነስት ኤንድ ያንግ የተባለው ተቋም ከጥቂት ዓመታት በፊት ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል፡፡ የተቋሙ መረጃ ትንቢት ሆኖ አልቀረም፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ሀገር ሆናለች፡፡
በዚህም በውጤታማ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ሪፎርም (Investment Policy Reform) እና የኢንቨስትመንት አቅም ትውውቅ (Promotion) ‹‹የ2017 ስታር ሪፎርመር ሽልማት (Star Reformer Award)››ን ከዓለም ባንክ ተቀብላለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሀገሪቱ የኢንቨስትመንት አቅሟን ለባለሀብቶች በማስተዋወቅና ፕሮጀክቶችን በማስፈፀም ረገድ ባከናወነችው ስኬታማ ተግባር ‹‹የ2017 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢንቨስትመንት ሽልማት (United Nations Investment Award) ››ን አግኝታለች፡፡
ኢትዮጵያ የውስጥ ሰላሟን የተረጋጋ ማድረግ መቻሏ ግጭትና አለመረጋጋት ዓይነተኛ መገለጫው በሆነው የአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ የቻለች አገር አድርጓታል፡፡ ይህም ከጎረቤት አገራት ጋር ያላትን ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር በማጠናከር ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡
የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ሀገሪቱ ባለፉት አስር ዓመታት ያስመዘገበችው የኢኮኖሚ እድገት በሚቀጥሉት ዓመታት ከእስከአሁኑ የተሻለ ዕድገት የማስመዝገብ ተስፋ እንዳላት ያሳያል፡፡
የኮሚሽኑ መረጃ እንደሚያሳየው፣ ባለፉት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያ ታላላቅ የዓለም የፋይናንስ ተቋማት ብሎም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የመሰከረላትና እነርሱንም ያሳመነ አስደናቂ የዕድገት ግስጋሴ አሳይታለች፡፡ ዋና ዋና የኢኮኖሚ አመላካቾችን መሰረት በማድረግ በሦስተኛው ሚሊኒየም የመጀመሪዎቹ ዘጠኝ ዓመታት የተመዘገበውን ዕድገት ለመመልከት እንደሚቻለው፣ ከ2000 እስከ 2008 ዓ.ም የአጠቃላይ ሀገራዊ ዕድገት ምጣኔ (GDP) በአማካይ 10 በመቶ ነው፡፡ ለአብነት ያህል በ2003 ዓ.ም 11 ነጥብ 4 በመቶ የሆነ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ተመዝግቧል፡፡ በዚህም የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከቀጣናውም ሆነ ከሌሎች አቻ አዳጊ ሀገራት የበለጠ ሥድገት አስመዝግቧል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ካስመዘገቡ ሀገራት መካከል ቀዳሚ ስፍራ ልትይዝ ችላለች፡፡
ታዲያ ይህ ሁሉ ኢኮኖሚያዊ እምርታ የተመዘገበው በአገሪቱ በሰፈነው ሰላም ምክንያት ነው፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ በኢኮኖሚው መስክ የተከናወኑ ተግባራትና የመጡ ለውጦች እንዲሁም አገሪቱ ያስመዘገበችው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በአገሪቱ የሰፈነው ሰላም ውጤቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ውጤቶችና ስኬቶችም የሀገሪቱን ሁለንተናዊ የግስጋሴ መሰረት በማደላደል ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ግብዓቶች ናቸው፡፡
ዛሬ የዓለምን ምጣኔ ሀብት በበላይነት የተቆጣጠሩት ሀገራት የውስጥ ሰላማቸውን በአስተማማኝነት የጠበቁና ትኩረታቸውን ልማት ላይ ያደረጉ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያም አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች ለሚስተዋሉ የሰላምና የፀጥታ መናጋቶች ዘላቂና አስተማማኝ እልባት መስጠት ከቻለች ባሰፈነችው ሰላም ምክንያት ያስመዘገበችውንም ምጣኔ ሀብታዊ እምርት አጠናክራ ማስቀጠል እንደምትችል አያጠያይቅም፡፡

 

አንተነህ ቸሬ

Published in ኢኮኖሚ

ቱርክ የአየር እና የባህር ኃይል ወታደሮችን በኳታር ለማስፈር እቅድ እንዳላት ማስታወቋን ተከትሎ ትንሿ አገር ከጎረቤቶቿ ጋር የገባችበትን ፖለቲካዊ ውዝግብ ሊያባብስ ይችላል የሚል ስጋት መፍጠሩ በስፋት እየተነገረ ነው፡፡ በኳታር የቱርክ አምባሳደር የሆኑት ፊክሬት ኦዘር ዶሃ ውስጥ በሰጡት መግለጫ፣ ቱርክ ከዚህ ቀደም በኳታር ካሰፈረቻቸው የእግረኛ ጦር ወታደሮች በተጨማሪ የአየር እና የባህር ኃይል አባል የሆኑ ወታደሮችን ለማስፈር እቅድ መያዟን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ አምባሳደሩ ወታደሮቹ ወደ ኳታር የሚላኩበትን ጊዜና ምን ያህል ወታደሮች ወደ ኳታር እንደሚላኩ ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡
እርምጃው የቱርክ እግረኛ ጦር፣ የአየርና የባህር ኃይል ወታደሮች በኳታር እንዲሰፍሩ እ.አ.አ በ2014 በቱርክና በኳታር መንግሥታት መካከል የተደረገው ስምምነት አካል እንደሆነም አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለወታደሮቹ የሚያስፈልጉት መሰረተ-ልማቶች ሁሉ እንዲሟሉና እርምጃው (ስምምነቱ) እንዲፈፀም አንካራና ዶሃ በጋራ እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡ ቱርክ በኳታር ወታደራዊ ካምፕ እንድትከፍት ሁለቱ አገራት ቀደም ብለው መስማ ማታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ቱርክ ይፋ ያደረገችው የወታደር ማስፈር እቅድም የሥምምነቱ አካል ነው ተብሏል፡፡
ቱርክ ለመጀመሪያ ጊዜ በኳታር ወታደሮቿን ያሰፈረችው እ.አ.አ በ2015 ነበር፡፡ ከዶሃ በስተደቡብ አቅጣጫ የሚገኘውና እስከ አምስት ሺህ ወታደሮችን የማስተናገድ አቅም ያለው ጣሪቅ ቢን ዚያድ የተባለው የቱርክ ወታደራዊ ካምፕ፣ ቱርክ በመካከለኛው ምሥራቅ የከፈተችው የመጀመሪያው ወታደራዊ ካምፕ እንደሆነ ይነገራል፡፡
ሳዑዲ አረቢያ፣ ግብፅ፣ ባህሬንና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኳታር ‹‹ሽብርተኝነትን ትደግፋለች›› በሚል ክስ እ.አ.አ ከሰኔ 5 ቀን 2017 ጀምሮ ከአገሪቱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቋረጣቸው ይታወሳል፡፡ እነ ሳዑዲ አረቢያም ከኳታር ጋር የገቡበትን ፖለቲካዊ ውዝግብ ለመፍታትና በኳታር ላይ የጣሉትን ማዕቀብ ለማንሳት ያስችላል ያሉትን መፍትሔ አቅርበው ነበር፡፡
በዚህ የመፍትሔ ሃሳብ ከተካተቱ ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ ኳታር በደቡባዊ ዶሃ የሚገኘውን ጣሪቅ ቢን ዚያድ የቱርክ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ እንድትዘጋ የሚጠይቅ ነው፡፡ ኳታርም ፈቃደኛ ሳትሆን ቀርታለች፤ እንዲያውም ተጨማሪ የቱርክ ወታደሮችን ለመቀበል አላቅማማችም፡፡
እነሳዑዲ አረቢያ ከኳታር ጋር ግንኙነታቸውን ካቋረጡበት ጊዜ ጀምሮ የፕሬዚዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶጋን ቱርክ የኳታር ዋነኛ አጋር ሆናለች፡፡ አንካራ ሁለቱን ወገኖች ለማሸማገል ጥረት ብታደርግም እስከአሁን ጠብ የሚል ነገር አልተገኘም፡፡ ይባስ ብለውም አገራቱ ከትንሿ አገር ጋር የሚዋሰኑባቸውንና የሚገናኙባቸውን የምድርና የባህር ድንበሮችን ሲዘጉ፣ ቱርክ የምግብ ሸቀጦችንና ሌሎች ቁሳቁሶችን የጫኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ አውሮፕላኖችን ወደ ዶሃ ልካ ነበር፡፡
ባለፈው ታኅሣሥ ወር ቱርክ ወታደሮቿን ወደ ኳታር መላኳ የሚታወስ ነው፡፡ በጊዜው የኳታር የመከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ ወታደሮቹ ወደ ኳታር የገቡት ሁለቱ አገራት እ.አ.አ በ2014 በተፈራረሙት ወታደራዊ ስምምነት መሰረት እንደሆነ አስታውቆ ነበር፡፡
በወቅቱ የቱርክ መንግሥት ባለሥልጣናት ቱርክ በቀጣናው ወታደሮቿን ማስፈሯ በአካባቢው ያለው የኃይል ሚዛን እንዲስተካከል ለማድረግ እንዲሁም ግጭቶችን ለማስቀረት እንደሚረዳና ቱርክ በኳታር ያላት ወታደራዊ ማዘዣ አገሪቱ በአካባቢው ያላትን ጥቅም ለማስጠበቅ እንጂ የትኛውንም አገር የማጥቃት ዓላማና ከአንዱ ወገን ጋር በማበር ድጋፍ የመስጠት ፍላጎት እንደሌላት ቢገልጹም፣ የቱርክ ድርጊት የባህረ ሰላጤውን ፖለቲካዊ ቀውስ ሊያባብሰው ይችላል በሚል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስጋቱን ገልጿል፡፡
እንግዲህ በዚህ ውዝግብ ላይ እያሉ ነው ቱርክ ተጨማሪ የአየር እና የባህር ኃይል ወታደሮችን ወደ ኳታር እንደምትልክ የገለጸችው፡፡ ይህም ኳታር ከአካባቢው አገራት ጋር የገባችበትን ፖለቲካ ውዝግብ እንዳያባብሰው ተሰግቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ልዕለ ኃያሏ አሜሪካ በደህንነትና በፀጥታ ጉዳዮች ከኳታር ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆኗን አስታውቃለች፡፡ ይህም ለባህረ ሰላጤው ፖለቲካዊ ቀውስ ሌላ ተጨማሪ ስጋት እንዳይፈጥር ተሰግቷል፡፡
የአሜሪካና የኳታር ከፍተኛ ባለሥልጣናት በዋሽንግተን ዲሲ ባደረጉት ውይይት፣ አሜሪካ በኳታር ሉዓላዊነትና ደህንነት ላይ የሚቃጡ ስጋቶችን ከኳታር ጋር በትብብር ለመመከት ዝግጁ መሆኗን ዋሽንግተን አስታውቃለች፡፡
የሁለቱን አገራት የውጭ ጉዳይ እና የመከላከያ ሚኒስትሮችን ጨምሮ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ በተካሄደው የሁለቱ አገራት ስትራቴጂካዊ ትብብር ውይይት አገራቱ በሰላምና ፀጥታ እንዲሁም በፀረ-ሽብርተኝነት ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት መስማማታቸው ተገልጿል፡፡
የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቶች በጋራ ያወጡት መግለጫ እንደሚያሳየው፣ አሜሪካና ኳታር በኳታር ሉዓላዊነት ላይ የሚሰነዘርንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተርን የሚፃረር ማንኛውንም ዓይነት ጥቃት በጋራ ለመከላከል ተስማምተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከፍተኛ ባለሥልጣናቱ ከባድ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የደህነት ተፅዕኖ ስላደረሰው የባህረ ሰላጤው ቀውስ ላይ ምክክር ማድረጋቸውንና፣ ኳታር ከጎረቤቶቿ ጋር የገባችበት ፖለቲካዊ ውዝግብ የኳታርን ሉዓላዊነት የማይጋፋ ፈጣን መፍትሔ እንደሚያስፈልግም መወያየታ ቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡ ሁለቱ አገራትም ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውንም መግለጫው ይፋ አድርጓል፡፡
የአሜሪካና የኳታር ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሁለትዮሽ ውይይቱን ያደረጉት ኳታር ውስጥ የሚገኘው የአሜሪካ የአየር ኃይል ማዘዣ የማስፋፊያ ግንባታዎች እንደሚያደርግ ይፋ ከሆነ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው፡፡ ዶሃ ውስጥ የሚገኘውና አል ኡዴይድ የተባለው የአሜሪካ ጦር ኃይል ማዘዣ ጣቢያ በአሁኑ ወቅት 10ሺ የአሜሪካ ወታደሮችን ያስተናግዳል፡፡
ኳታር ከአሜሪካ በርካታ የጦር መሳሪያ ከሚገዙ አገራት መካከል አንዷ ስትሆን፣ በሁለቱ አገራት መካከል የተፈረመው የጦር መሳሪያ ግዢ ስምምነት 24 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ይነገራል፡፡
ታዲያ አሜሪካና ኳታር ያደረጉት የሰሞኑ ውይይት ኳታር ከጎረቤቶቿ የባህረ ሰላጤው አገራት ጋር የገባችበትን ፖለቲካዊ ውዝግብ እንዳያባብሰው ተሰግቷል፡፡ አሜሪካ ከኳታር ጋር ከፍተኛ ገንዘብ የሚያወጣ የጦር መሳሪያ ግዢ ስምምነት መፈራረሟ፣ እና ሳዑዲ አረቢያ ‹‹ሽብርተኞችን ትደግፋለች›› በሚል ክስ ግንኙነታቸውን አቋርጠው ሳለ አሜሪካ ግን ባለፈው ሐምሌ ወር የኳታርን የፀረ-ሽብርተኝነት ዕርምጃዎች ማድነቋ እንዲሁም የልዕለ ኃያሏ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን ወደ ዶሃ በተደጋጋሚ ተጉዘው ከኳታር ባለሥልጣናት ጋር መገናኘታቸው እነሳዑዲ አረቢያን አላስደሰተም፡፡
እነሳዑዲ አረቢያ ‹‹አሜሪካ ለኳታር ወግናለች›› ብለው በአሜሪካ ድርጊት ቅር ሲሰኙ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ደግሞ የአሜሪካና የኳታር ግንኙነት አሜሪካ በኳታር ላይ የተለሳለሰ አቋም እንዲኖራት በማድረግ የባህረ ሰላጤውን ቀውስ ያባብሰዋል የሚል ስጋት አድሮባታል፡፡
ኳታር እንዲሁም ሳዑዲ አረቢያ በፊታውራሪነት የምትመራው የአገራት ቡድን የፈጠሩት የፖለቲካ ውዝግብ ለወትሮውም ቢሆን ግጭትና ፖለቲካዊ ሽኩቻ ለማያጣው የመካከለኛው ምሥራቅ ቀጣና ተጨማሪ የደህንነትና የፀጥታ ስጋት ፈጥሯል፡፡
(ምንጭ፦ አልጀዚራ)

አንተነህ ቸሬ

Published in ዓለም አቀፍ

የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት በዓለም እምቦ ቃቅላ ዕድሜ ካላቸው አዳጊ ሥርዓቶች ውስጥ የሚመደብ ነው። ይህ ሥርዓት በኢትዮጵያ ውስጥ ሲጀመር ከአስከፊ የድህነትና የዴሞክራሲ እጦት ደረጃ ላይ በመነሳት ነው። ይህ ብቻም አይደለም! ሥርዓቱ ሲጠነሰስ በፀጥታና መረጋጋት ችግር ውስጥ ይታመስ ከነበረው የምሥራቅ አፍሪካ ጂኦፖለቲካ ውስጥ ሆኖ ነበር። ይህም ሆኖ ሳለ ግን የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት በርካታ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ስኬቶችን በማስመዝገብ ለሌሎች አገራት የሚተርፉ ልምዶችን ሊያበረክት ችሏል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት ሁሉም የዓለም ፌዴራል አገራት የሚከተሏቸውን የጋራ ባህሪያት ያሟላ ነው። የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት ከራሱ ታሪካዊና ነባራዊ ሁኔታዎች የመነጩ ልዩ ባህሪያት አሉት። የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት በሁሉም የዴሞክራሲያዊ ይዘት መስፈርቶች ሲመዘን የላቀ ዴሞክራሲያዊነት ያለውን ህገ መንግሥት በማፅደቅ እየተመራ የሚገኝ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት የተረጋገጡ መብቶችና የአፈፃፀም አቅጣጫዎችን በተመለከተ ከብዝሃነት አያያዝ አንጻር ሲገመገም በጥልቀት አልተመረመረም፤ በቂ ትምህርትም አልተወሰደበትም የሚሉ አስተያየቶች ይደመጣሉ።
አንዳንዶች የፌዴራል ሥርዓቱ የብዝሃነት አያያዝ አፈፃፀሞች ግጭቶችን እያባባሱና አንድነትን አደጋ ላይ እየጣሉ፣ ለብሄር ቅራኔዎች መጧጧፍ ምክንያት እየሆኑ ናቸው የሚሉ ሃሳቦችን ያራምዳሉ። በአሁኑ ጊዜ የህብረ ብሄራዊነት ግንባታ ሂደትን የሚፈታተኑ ተግዳሮቶች ጎልተው እየታዩ ናቸውም ይላሉ፡፡ በሌላ ወገን በኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት የህብረ ብሄራዊነትን ምንነት በመገንዘብ የግንባታ ሂደቱን ማሳካትና ችግሮችን በመታገል የኢትዮጵያን የህዳሴ ጉዞ እውን ማድረግ ያስፈልጋል የሚሉም አሉ።
ህገ መንግሥት የአንድ አገር መሠረታዊ ህግ ነው በሚለው ትርጓሜ ብዙዎች ግን ይስማማሉ። አገላለጻቸው ይለያይ እንደሆን እንጂ ሁሉም ፀሐፊዎች ህገ መንግሥት የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ መሆኑን ይስማማሉ፡፡ ህገ መንግሥት የአንድ አገር ህዝብ ስለፖለቲካዊ ሥርዓቱና አስተዳደሩ ያሳለፈውን ውሣኔና ስምምነት የሚወክል የህግ ማዕቀፍ ነው፡፡ የህዝቦች የስምምነት መንፈስና ለስምምነቱ የተሰጠውን ክብደት፣ የመንግሥትን የሥልጣን ህጋዊነት፣ የሥርዓቱን ባህሪያት የሚወስን ነው፡፡ በመሆኑም ሌሎች ህጎች የሚመነጩት፣ እውቅናና ተፈፃሚነት የሚያገኙት ከዚሁ ህገ መንግሥት ነው፡፡
ከህገ መንግሥት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ጉዳይ ህገ መንግሥታዊነት ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ህገ መንግሥታዊነት ከአስተሳሰብና እምነቶች፣ ከእሴቶችና መርሆች ጋር የተያያዘ ትርጉም ሲሰጠው ይታያል። በህገ መንግሥት የመገዛትን እምነት፣ ዜጎች ሊላበሷቸውና ወደቀጣይ ትውልዶች ሊያስተላልፏቸው የሚገቡ ህገ መንግሥታዊ መርሆዎችንና እሴቶችን ወዘተ…ወደ ባህል ደረጃ በማሳደግ የተረጋጋ ኅብረተሰብንና ዋስትና ያለው የፖለቲካ ሥርዓት ግንባታን ለማሳካት የሚያስችል መሣሪያም ስለመሆኑ ስምምነት አለ።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ቁም ነገር ደግሞ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓት ህገ መንግሥትና ህገ መንግሥታዊነት በተግባር የሚተረጎሙበት መሆኑ ነው፡፡ በአንድ በኩል በህገ መንግሥት የተደነገጉትን ዓላማዎች፣ እሴቶች፣ መርሆዎች፣ መብቶች፣ ግዴታዎች እና ሌሎችም ድንጋጌዎች በተግባር ተፈፃሚ የሚደረጉበት ሥርዓት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ህገ መንግሥታዊነትን ለማስፈን የሚከናወኑ ቀጣይነት ያላቸው ሥራዎችን ለመተግበር ምቹ ምህዳር የሚፈጠርበት ነው፡፡
በኢትዮጵያ የነበሩት ህገ መንግሥቶች የተሟላ ቅርፅ ባይኖራቸውም የበላይ ህግ ተደርገው ሥራ ላይ የዋሉ በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ህጎች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ህጎች ውስጥ ፍትሐ ነገሥት እና ክብረ ነገሥት ተጠቃሾች ናቸው። ከ1923 ዓ.ም አንስቶ የተለያዩ ይዘቶች ያሏቸው ሦስት ሕግጋተ መንግሥት ሥራ ላይ ውለዋል፡፡ እነዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ በ1923 ዓ.ም ሥራ ላይ የዋለው የንጉሠ ነገሥት ህገ መንግሥት ነው። ይህንን ህግ በማሻሻል በ1948 ዓ.ም የፀደቀው እና በወታደራዊ ደርግ መንግሥት ሥራ ላይ የዋለው የ1980 ዓ.ም ህገ መንግሥቶችም ቀሪዎቹ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በመንግሥትና በዜጎች መካከል የሚኖርን ግንኙነት፣ የሥልጣን ባለቤትነትና የመንግሥት አወቃቀር መልክ የወሰነው ህግ የአፄ ኃይለሥላሴ ህገ መንግሥት ነው፡፡ ይህ ህገ መንግሥት ንጉሠ ነገሥቱ በመለኮታዊ ኃይል ተመርጠው እንደተሾሙና በፈቃዳቸው ህገ መንግሥቱን ለሕዝቡ እንደሰጡ በግልጽ የተደነገገ ህገ መንግሥት እንደነበር የታሪክ ድርሣናት ያስረዳሉ። የሥልጣን ምንጭ መለኮታዊ ኃይል በመሆኑ የህዝብ ይሁንታ እንደማያስፈልግና ህገ መንግሥቱም የህዝቦች የቃል ኪዳን መገለጫ ሳይሆን በመለኮታዊ ኃይል የተሰየሙት ንጉሠ ነገሥት በፈቃዳቸው ለህዝቡ ያበረከቱለት ስጦታ እንደነበር ያመለክታል፡፡ የሥልጣን ባለቤትነት ከነገሥታቱ ሳይወጣ በዘር ሐረግ የሚተላለፍ እንጂ ህዝብ ለመረጠው አካል አይሰጥም። ከዚህም ባለፈ ሥርዓቱ ያነገሠው አስተሳሰብ ህዝቡ የንጉሡ ሀብት ንጉሡም የፈጣሪ ተወካይ መሆናቸውን እንዲታመን ማድረግ ነው፡፡
በ1948 ዓ.ም ተሻሽሎ የፀደቀው ህገ መንግሥ ትም ቢሆን መሠረታዊ የይዘትና የዴሞክ ራሲያዊነት ለውጥ አላመጣም፡፡ ኢትዮጵያን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ለማድረግ፣ ኤርትራን ከኢትዮጵያ በኮንፌዴሬሽን ለማቀላቀልና ምዕራባዊ አስተሳሰብ የህገ መንግሥቱ እሴት መሆኑን ለማመላከት ሲባል ብቻ ህገ መንግሥቱ እንደተሻሻለ ይገልጻል፡፡ በሁለቱም ህገ መንግሥታት ንጉሡ የህግ አውጪነት፣ የህግ አስፈፃሚነትና የህግ ተርጓሚነት ሥልጣን ባለቤት ነበሩ፡፡
የደርግ ወታደራዊ ጁንታ ወደ ሥልጣን የመጣው በ1967 ዓ.ም ላይ ነበር። ደርግ ህገ መንግሥት ያወጣው ደግሞ በ1980 ዓ.ም ነበር፡፡ ደርግ ፍፁም ፀረ ዴሞክራሲያዊ ስለነበር ህዝቡ በተወካዮቹ አማካይነት በህገ መንግሥቱ ማርቀቅም ሆነ በረቂቁ ላይ በቀጥታ በመምከር ወይም በወኪሎቹ በኩል በህገ መንግሥታዊ ጉባዔ ህገ መንግሥቱን በማፅደቅ ሂደት ያደረገው ተሳትፎ አልነበረም፡፡ ደርግ ይከተለው በነበረ ርዕዮተ ዓለም ምክንያት በህገ መንግሥቱ የሠርቶ አደር ህዝብን (የላብ አደርን) የበላይነት ቢደነግግም የርዕዮቱ መሠረት ሊሆን የሚችል ላብ አደር አልነበረም። በተጨማሪም ደርግ የደነገገውን የላብ አደሩን የሥልጣን ባለቤትነት ከህገ መንግሥቱ በፊትና በኋላ በወጡ ህጎች በግለጭ አግዷል፡፡ በቀጣይ ወደ ኢፌዴሪ ህገ መንግሥት መለስ ብለን ልዩ ባህሪያቱን በጥቂቱ እንዳስስ።
የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት የአገሪቱን ታሪካዊና ነባራዊ ሁኔታ መሠረት ያደረገና የህዝቦችን መሠረታዊ እምነቶችና ፍላጎቶች የሚወክል ህግ በመሆኑ ከሌሎች የዓለም ምርጥ ህገ መንግሥት አንዱ ያደርገዋል፡፡ ህገ መንግሥቱ ከአገሪቱ ታሪካዊና ነባራዊ ሁኔታ የመነጩ ልዩ ባህርያትንም ይዟል፡፡ ከእነዚህም መካከል የዴሞክራሲያዊ ገፅታ መገለጫዎቹ ተጠቃሽ ይሆናሉ።
የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ከቀደሙቱ በመሠረቱ የተለየና ዘመናዊ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የኢትዮጵያ ህዝቦች በየአካባቢያቸው ተወያይተውና ተከራክረው የተስማሙበትና በመረጧቸው ወኪሎች አማካይነት በተቋቋመው ህገ መንግሥታዊ ጉባዔ የበላይ ህግ ሆኖ እንዲፀድቅ ማድረጋቸው ልዩ ያደርገዋል፡፡ ይህም በዓለም አቀፍ መስፈርት ሲመዘን ዘመናዊ የአቀራረፅ ሂደት የተከተለ መሆኑን ያሳያል፡፡ በህገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ እንደተገለጸው ሥርዓቱ የተመሠረተበት አስተሳሰብ ወይም ፍልስፍና፣ የሚመራባቸው ራዕይና ዓላማዎች ካለፈው የታሪክ ምዕራፍ በዓይነቱ የተለየ ነው፡፡ ህገ መንግሥቱ ያረጋገጣቸው መብቶች በዓለም አቀፍ መስፈርት ሲታዩ የላቀና ዘመናዊ መሆኑን ያሳያሉ፡፡ በህገ መንግሥቱ ከሰፈሩት 106 አንቀፆች ውስጥ አንድ ሦስተኛው ገደማ ስለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተደነገጉበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችም የህገ መንግሥቱ አካል ሆነዋል፡፡ በተጨማሪም የህገ መንግሥቱ የማሻሻያ ሥርዓት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በቀላል ማሻሻያ እንዳይሸራረፉ ዋስትና ሰጥቷል። የዚህ ህገ መንግሥት ሌላው ባህሪያቱ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት መፍቀዱ ነው።
ይኸውም የህገ መንግሥቱ አንዱ ልዩ ባህሪ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት ማረጋገጡ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች የታገሉለት ዋነኛው ዓላማ የራስ አስተዳደርና የጋራ አስተዳደርን የመመሥረት መብት ለመጎናፀፍ፣ ይህም ከተፅዕኖ ነፃ በሆነ መንገድ በፈቃደኝነትና በመተማመን ላይ የተደራጀ ዘላቂ አብሮነት መመሥረት ነው፡፡ ሁለተኛው ዓላማ ይህን መብት በማንኛውም አጋጣሚ ሲቀለበስ ወደቀድሞው የአፈና ሥርዓት ላለመመለስና በሠላማዊ መንገድ ለመፋታት የሚያስችል ፖለቲካዊ ምህዳር ለመፍጠር ነው፡፡
የድንጋጌው መነሻ አብሮ ለመኖር አፈና እንደማያስፈልግ፣ አብሮነቱን ያልፈለገ ማኅበረሰብ ደግሞ ከህብረቱ ለመውጣት በግጭትና በጦርነት መሸኘት የለበትም የሚል መሠረታዊ እምነት ነው፡፡ የመገንጠል መብት ሲያነሱ የነበሩ ማህበረሰቦችና ኃይሎች ይህ መብት በህገ መንግሥት ከተረጋገጠ በኋላ በተግባር በህብረቱ መቀጠላቸውን፣ በጠባብነት አጀንዳ በመሰለብ የመገንጠል ጥያቄ አለን የሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ፍላጎትም የህዝብ አመኔታ እያጣ መምጣቱ የሚያረጋግጠው ጉዳይ በእኩልነትና በነፃነት ላይ የተመሠረተ አብሮነትና ሕብረ ብሄራዊነት ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ጥቅሞች ማምጣት እንደቻለ ነው፡፡
የግለሰብና የጋራ መብቶችን ያጣመረ መሆኑም ሌላው የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ባህሪያት ሆነው ይቀርባሉ። የግለሰብና የጋራ መብቶች በበርካታ አገራት ህገ መንግሥታት ጥበቃ ለማድረግ ይሞከራል፡፡ ነገር ግን በአተገባበራቸው ላይ ከአገር አገር ሰፊ ልዩነቶች ይታያሉ፡፡ የግለሰብ መብት ሲከበር እግረ መንገዱን የጋራ መብትም ይከበራል የሚልና የጋራ መብቶች ተለይተው ከተረጋገጡ የግለሰብን መብቶች ለማፈን መሣሪያ ይሆናሉ የሚል አስተሳሰብ ገዥ ቦታ ይዞ ይገኛል፡፡
የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ከዚህ አስተሳሰብ በዓይነቱ የተለየ እምነትን መነሻ በማድረጉ ሁለቱን መብቶች ሙሉ ጥበቃ ያደርግላቸዋል፡፡ ህገ መንግሥቱ በአንድ በኩል እነዚህ መብቶች በአገሪቱ ሁኔታ ተነጣጥለው ሊሄዱ የሚችሉ አይደሉም ብሎ ይወስዳል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአንዱ መብት መከበር ስም የሌላው መብት እንዲረገጥ ቦታ የሚሰጥ አይደለም፡፡ በአፈፃፀም ሂደትም አንዱን መብት ለማስጠበቅ ሲባል ሌላውን መብት መደፍጠጥ አያስከትልም፡፡ የቡድን መብቶች የሚፈለጉትና ፋይዳ የሚኖራቸው እንደ ቡድን ተገቢውን የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሀብትና የማህበራዊ ጥቅሞችን ለማረጋገጥ ነው፡፡ የቡድን መብቶች የማንነት የጋራ መገለጫዎች በመሆናቸው በተናጠል በግለሰብ ደረጃ ተጠይቀው መልስ ሲሰጣቸውና በዚህ አማካይነትም የቡድን መብቶች መፍትሔ ሊያገኙ አይችሉም፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ አንስቶ «መሬት ላራሹ» በሚል መፈክር ወሣኝ ትግል አካሂዷል፡፡ ህገ መንግሥቱ ይህንን ጥያቄ የመለሰበት መንገድ በዓለም ከታዩ ልምዶች በዓይነቱ የተለየ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የመሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት መሆኑን በመጥቀስ «መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦች ህዝቦች የጋራ ንብረት ነው» የሚል ድንጋጌ አስፍሯል፡፡ በአገሪቱ ሁኔታ መሬት ዋነኛ የሀብት ምንጭ በመሆኑ አርሶ እና አርብቶ አደሮች በመሬት ላይ ያልተገደበ የመጠቀም መብት ተጎናፅፈዋል፡፡ ተጠቃሚው አርሶ አደር ወይም አርብቶ አደር ራሱ ተጠቅሞ ለልጆቹ የማስተላለፍ መብትም ተረጋግጦለታል፡፡ በመሬቱ ላይ ሠርቶ፣ ጥሮና ግሮ ገደብ የሌለው ምርት የማፍራትና ምርቱን በነፃ ገበያ በመረጠው ዋጋ የመሽጥ መብቱ ያለገደብ ተረጋግጦለታል፡፡ መሬት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት በመደረጉ ከመሬት ያለመነቀል ዋስትና የሚሰጥና የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጫ መሣሪያ ሆኗል፡፡
ሌላው የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ባህሪያት ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል በቁጥር አናሳ የሆኑ ህዝቦች እንደ ሌሎቹ ማኅበረሰቦች በቋንቋቸው የመጠቀም፣ ታሪካቸውን የመግለጽ፣ ባህላቸውንና ልዩ መገለጫዎቻቸውን የማሳደግና የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት ማረጋገጡ ነው። በፌዴሬሽን ምክር ቤት ፍትሐዊ ውክልና የማግኘት መብታቸው ዋስትና አግኝቷል፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ከ20 የማያንስ መቀመጫ እንዲኖራቸው በህገ መንግሥቱ ተደንግጓል፡፡ ይህ መብት በአሁኑ ጊዜ አናሳ ማኅበረሰቦች በተወካዮች ምክር ቤት በ23 መቀመጫ እንዲወከሉ አስችሏል፡፡ አናሳ ማኅበረሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የምጣኔ ሀብትና ማህበራዊ ዓላማዎች በህገ መንግሥቱ ላይ ሰፍረዋል፡፡ ይህም የሚያሳየው ፌዴራል ሥርዓቱ አናሳ ማኅበረሰቦች የመብት ጥያቄዎች እስኪያነሱ ድረስ ሳይጠበቅ ህገ መንግሥቱን ከጅምሩ ለፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ መብቶቻቸው የተሟላ መልስ መስጠቱ ነው፡፡ ይህ ነው የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ከሌሎች ተመራጭ ብቻ ሳይሆን የተለየ ነው ብሎ በድፍረት ለመናገር የሚቻለው።

አባ መላኩ

Published in አጀንዳ

በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩ ክቡር ሰማዕታት የደምና ህይወት ዋጋ ሀገራችን የዴሞክራሲ፣ የልማትና የብልጽግናን መስመር ይዛ መንጎድ ከጀመረች አስርት ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ በዚህ ሂደት ብዙ የችግር ማጦችን ተሻግረን ተቀብረንበት ከነበረው የድህነት አረንቋ አንገታችንን ቀና አድረገን የብልጽግናን አድማስና መዳረሻ መመልከት ችለናል፡፡
ዛሬ ዓለም ስለእኛ የሚያወራው ተራቡ፣እርስ በርስ ተላለቁ፣ የኋላቀርነት ምሳሌ ናቸው ብሎ ሳይሆን በሰላሟ ተመራጭና ለአፍሪካውያንም መከታ የሆነች፣ በኢኮኖሚ ዕድገትና ብልጽግና ከቀዳሚዎች ተርታ ፊት የተሰለፈች ሀገር በማለት ሆኗል፡፡
የአንድ ብሄር የበላይነትን እንዳይፈቅድ ሆኖ የተገነባው ፌዴራላዊ ስርዓታችን ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቤተኛ አድርጓቸው ለልማቷ በአንድነት ለመትጋት ለሉዓላዊነቷ በጋራ ለመቆምና ለመሰዋት የቆረጡ ህዝቦች ሀገር አድርጓታል፡፡ ክብር ለፌዴራላዊ ስርዓታችን ይሁንና ዛሬ ኢትዮጵያ በቀላሉ የምትቆረጠም ጥሬና በአፍራሽ ኃይሎች ጩኸት የምትበታተን ሀገር ሳትሆን ስትናገር ብዙ ሰሚ ጆሮ ያላት ከራሷም አልፋ ለጎረቤትና ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮችም የሰላም ጠበቃ የሆነች ታላቅና ክቡር ሀገር ሆናለች፡፡ በጀግናው የመከላከያው ሠራዊታችን የሰላም ማስከበር ተልዕኮ እልቂት ስጋት ድነው በአንፃራዊነት ሰላማዊ እንቅልፍን የሚተኙ እልፍ አፍሪካውያንም የፌዴራላዊ ስርዓታችን ፍሬ ተቋዶሾች ናቸው፡፡
ለዘመናት የተከመረብን ድህነትና ሳንሠራ እርስ በርስ ስንተላለቅ የኖረንበት ዘመን ያሸከመን የልማት የቤት ሥራዎች በርካታ ናቸውና ህዝቦችን አሁን ለሚፈልገው ደረጃ የሚመጥን ሀብት አላፈራንም። ዴሞክራሲያችንም ብዙሃነትን መሰረት ያደረገና በእንጭጭ ደረጃ ያለ በመሆኑም በሚፈለገው ልክ የህዝቡን ጥማት አስታግሷል ተብሎ አይወሰድም፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም በተግባር ግብዓተ መሬታቸው የተፈፀመ በአስተሳሰብ ግን ከአንዳንድ ጥገኞች አዕምሮ ያልተፋቁ የጠባብነትና የትምክህት አስተሳሰቦችም አሁንም የሀገሪቱ የህዳሴ ጉዞ ደንቃራ ሆነው አፈር ልሰው ለመነሳት የሚውተረተሩበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡
በዚህ ሂደት የሥራ ዕድል ይፈጠርልኝ፣ ከአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር የሚመጣጠን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ይስፈን፣ ዴሞክራሲ ይዳብርን የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ማንሳት ተገቢም አስፈላጊም ነው፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች በአንክሮ ማድመጥና ተገቢውን ምላሽ መስጠትም ከመንግሥት የሚጠበቅ ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት ነው፡፡ ይሁንና ይህንን አስታኮ በስመ «የመልካም አስተዳደር ችግር አለ»፣«በቂ የሥራ ዕድል አልተፈጠረልኝም» ወዘተ መነሻነት የልማት አውታሮችን ማፍረስ፣ ዘር እየለዩ ዜጎችን ማሳደድና ማጥቃት ግን ከኢትዮጵያዊነት እሴትና ባህል ያፈነገጠ፣ ዕድገታችንን የሚያጠለሽ የጨለምተኝነትና የእኩይነት መገለጫ ነው፡፡ ልማትን እያወደሙ በቂ መሰረተ ልማት አልተገነባልኝም፣ በዜጎች ላይ የብሄር ተኮር ጥቃት እየፈፀሙ መብቴ በበቂ ስላልተከበረልኝ የሚል ሰይጣናዊ ተግባር ግን በማንኛውም መልኩ በጥብቅ የሚወገዝና አስፈላጊውና አስተማሪ ቅጣት ሊጣልበት የሚገባ አስፀያፊ ተግባር ነው፡፡
በቅርቡ በሀገራችን በአንዳንድ አካባቢዎች በተነሱ ግጭቶችም በድሃ አቅማችን የገነባነውን ታላላቅ የልማት አውታሮችና የግለሰቦችን ሀብት የማውደም ብሎም ዜጎችን በማንነታቸው እየለዩ ማጥቃትን የመሳሰሉ እርኩስ ተግባራት መከሰታቸውን ከየአካባቢው የሚወጡ መግለጫዎች ያመለክታል፡፡
ይህ እኩይ ተግባር ሰይጣናዊ አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ጥቂት የጥፋት ኃይሎች ሥራ ቢሆንም ለዘመናት ተፈቃቅረውና ተቻችለው እንኳን የሀገራቸው ልጅ የሆነን ኢትዮጵያዊ ቀርቶ ለየትኛውም የአዳም ዘር በችግር ጊዜ ጥላ ከለላ በሆኑ ጨዋና ታላቅ የሀገራችን ህዝቦች ላይ ጥሎት የሚያልፈው ጠባሳ በቀላሉ የሚፋቅ አይሆንም፡፡ ይህንን ተግባር የሚፈጽሙ ኃይሎችም ያለምንም መሸፋፈንና መደባበቅ እኩይ ተግባራቸውን ከሚወሰድባቸው ተገቢና ህጋዊ ቅጣት ጋር በይፋ ካልተገለጹ በህዝቦች ትስስርና በሀገራዊ ህልውናችን ላይ ሊፈጥር የሚችለው ፈተና ከግምት በላይ ነው፡፡ ከእዚህ የጥቂት የጥፋትና ከኢትዮጵያውያን ባህልና እሴት ያፈነገጠ ተግባር በተቃራኒው ዜጎች በማንነታቸው የተነሳ ጥቃት እንዳይደርስባቸው ፊት ለፊት ተጋፍጦ በመከላከልና ተጎጂዎችን በመርዳትና በማቋቋም ብሎም ከመከላከያና የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ወጣቶችን ከስሜታዊነት እንዲርቁ በመምከርና ሁከትን በመከላከል ረገድ በርካታ ዜጎች ያደረጉት በጎና ኢትዮጵያዊነትን የሚመጥን ተግባር ምስጋና ሊቸረውና አርአያነቱና ትምህርታዊነቱ በሌሎችም ይሰርጽ ዘንድ ሊጎላ የሚገባው ነው፡፡
እርግጥ ነው! የኢትዮጵያ ህዝብ ክቡር ህዝብ ነው! ስለዚህም ነው ለዚህ ክቡር ህዝብ ልዕልና እና ህልውና ሺዎች በጀግንነት ህይወታቸውን የሰጡትና እየሰጡም ያለው። የዚህን ክቡርና ታላቅ ህዝብን ጥያቄና ፍላጎት ማዳመጥና ተገቢውን ምላሽ መስጠት ምንጊዜም ወደ ኋላ ሊባል የማይቻል ተግባር ነው፡፡ ይሁንና እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባ ዋና ጉዳይ ግን ህዝቡ የሚያነሳው ጥያቄ ሁሉ በአንድ ጀንበር ምላሽ የሚሰጥበትና የሚፈታ ሳይሆን ከሀገሪቱ አቅም ጋር ተያይዞ ወዲያውኑ የሚፈታው ወዲያው፤ አቅምና ጊዜን የሚጠይቀው ደግሞ ጊዜውን ጠብቆ በተገቢው መንገድ የሚፈታ መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም ህዝቡም ይሄን ጉዳይ በሚገባ ማጤንና ጥያቄዎችን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ብቻ ማቅረብ ሁሌም ሊተገብረው የሚገባው ጉዳይ ሊሆን ይገባዋል፡፡
ያለፉት 26 ዓመታት ታሪካችን መንግሥትና ህዝብ ከተቀራረቡና ከተወያዩ የማይፈቱት ችግር እንደሌለ በትልቁ አስተምሮናል፡፡ በእስካሁኑ ሂደታችንም የሀገሪቱ ሰላምና ደህንነት ተጠብቆ እዚህ ደረጃ የተደረሰውም ተግዳሮቶች ጠፍተውና መንገዱ ሁሉ አልጋ ባልጋ ሆኖ ሳይሆን በገጠሙ ችግሮች ዙሪያ መንግሥትና ህዝብ በአንድ ላይ ተቀምጠው ስለመከሩና የጋራ የመፍትሔ አቅጣጫም አስቀምጠው በጋራ በመንቀሳቀሳቸው ነው፡፡
ሀገራችን ብዝሃነት ያለባትና በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የምትገኝ ሀገር እንደመሆኗ ዛሬም ሆነ ወደፊት የህዝብ የልማት፣የዴሞክራሲና የተጠቃሚነት ጥያቄ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጥርጣሬ የለም፡፡ እነዚህን ጥያቄያዎችም በዴሞክራሲያዊ አግባብ በውይይት እየፈቱ የሀገርን ህልውና ሰላም አጠናክሮ ማስቀጠሉ ለአፍታም ቸል ሊባል አይገባም፡፡ ከዚህ በተቀራኒው ግን በስመ የህዝብ ጥያቄ እጅን ወደሀገርና ህዝብ ሀብት ውድመት መሰንዘር ብሎም ዜጎችን ብሄር ለይቶ የማጥቃት እኩይ ተግባር ግን እንዳይደግም ተደርጎ ለአንዴና ለመጨረሻ አስተማሪ እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል እንላለን፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።