Items filtered by date: Saturday, 03 February 2018
Saturday, 03 February 2018 23:58

የፌስቡክ ቋንቋ

ማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች በአጭር ዓመታት ውስጥ በዓለም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠር ችለዋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያም ካየን በአሁኑ ጊዜ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከፍተኛ ተከታይ አላቸው፡፡ ከእነዚህ ማህራበዊ የመገናኛ ዘዴዎች ውስጥ በስፋት የወጣቱን ቀልብ የተቆጣጠረው ግን ፌስቡክ ነው፡፡
ፌስቡክ በጣም ብዙ ተብሎለታል፡፡ በመድረክም ይሁን በዋናዎቹ የመገናኛ ብዙኃን ስለፌስቡክ ጠንካራም ሆነ ደካማ ጎን ብዙ ተብሏል፡፡ ክርክሮችም ነበሩበት፡፡ ክርክሮቹ ግን የተለያዩ አይነት ናቸው፡፡ መጀመሪያ ፋሽን በነበረበት ጊዜ የነበረው ክርክር ‹‹ጊዜን ያባክናል እንጂ ምንም አይጠቅምም›› የሚሉ እና ‹‹በራሱ ማንበብ ስለሆነ ጊዜን ማባከን አይደለም›› የሚሉ ነበሩ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ‹‹ውሸትና አሉባልታ የሚነዛበት ነው፣ ብሄርን ከብሄር እያጋጨ ነው›› የሚሉ እና ‹‹መደበኛዎቹ የመገናኛ ብዙኃን በጣም ይዘገያሉ፣ እውነቱን አያሳውቁም፤ ስለዚህ ፌስቡክ አማራጭ ነው›› የሚሉ ናቸው፡፡
ለሁሉም ክርክሮች እንደ አስታራዊ የሚወሰደው ሀሳብ ‹‹እንደ አጠቃቀሙ ነው›› የሚለው ነው፡፡ እርግጥ ነው እንዳጠቃቀሙ ነው፤ ግን የሚያጠፋው ከበለጠ ደግሞ ችግር ነው፡፡ እንደ አጠቃቀሙ ነው የሚባለው ለግለሰብ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ ጥሩ ጥሩ ነገር ብቻ እየፈለኩ የማነብበት ከሆነ፣ ጊዜዬን በአግባቡ የምጠቀምበት ከሆነ ጠቀሜታው ለእኔ ብቻ ነው፡፡ እንደ አገር እያስከተለ ያለውን ችግር ማስቀር የሚቻለው ሁሉም ባይሆን እንኳን ቢያንስ አብዛኛው በአግባቡ ቢጠቀም ነበር፡፡
ለማንኛውም ፌስቡክ እያስከተለ ካለው አሉታዊ ችግር ውስጥ እኔ መታዘብ የፈለኩት የቋንቋ አጠቃቀምን ነው፡፡ ይሄ ነገር ብዙም ትኩረት የተሰጠው አይመስለኝም፡፡ዳሩ ግን ፌስቡክ ቋንቋን በጣም እያበላሸ ነው፡፡ ውሸት እየተደጋገመ ሲሄድ እውነት መምሰሉ ግልጽ ነው፡፡ ስህተት በጣም በተደጋገመ ቁጥር ልክ ሊመስል ይችላል፡፡
በጣም የሚያሳዝነው ነገር ፌስቡክ ላይ ያለውን የተሳሳተ የቋንቋ አጠቃቀም በጋዜጦች፣ መጽሔት፣ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ላይ ያሉ ጋዜጠኞችም መጠቀም መጀመራቸው ነው፡፡ በዚህ አሥር ዓመት እንኳን ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ፌስቡክ ይህን ያህል ጥፋት ማድረስ ከቻለ በአርባና ሃምሳ ዓመታት ውስጥ አንድን ቋንቋ ሙሉ በሙሉ ላለማውደሙ እርግጠኞች አይደለንም፡፡
ስህተቱ እኮ እዚያው ፌስቡክ ላይ ብቻ ቢቀር ባልከፋ ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ጋዜጠኛውም፣ ባለሥልጣኑም፣ ምሁሩም የፌስቡክ ተጠቃሚ ቢሆንም በብዛት የሚጠቀሙት ግን ወጣቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ወጣቶች ደግሞ ለቋንቋ አጠቃቀም ግዴለሽ እየሆኑ ነው፡፡ ጋዜጠኛው ይህን ነገር ማስተካከል ሲገባው ጭራሽ በመገናኛ ብዙኃንም ፌስቡክ ላይ በለመደው እየተጠቀመ ለሚሊዮን ህዝብ ያዳርሳል፡፡ አሁን ላይ እኮ ጋዜጦችና መጽሔት ላይ፣ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ላይ ጸያፍ የቃላት አጠቃቀም እያየን ነው፡፡
ለምሳሌ ‹‹መጣህ›› ለማለት ‹‹መጣክ›› ‹‹በላህ›› ለማለት ‹‹በላክ›› እያሉ መጠቀም እየተለመደ መጥቷል፡፡ በሌላ በኩል አግባብ ያልሆኑ አብዢ ቅጥያዎችን ማየትም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፌስቡክ ያስፋፋው ስህተት ነው፡፡ ‹‹መጣችሁ›› ለማለት ‹‹መጣቹ›› ወይም ደግሞ ‹‹መጣችው›› የሚባልም አለ፡፡ ምናለ ስህተቱ እንኳን አንድ አይነት ቢሆን? ‹‹እመጣለሁ›› ለማለት ‹‹እመጣለው›› እያሉ መናገርና መፃፍ እየተለመደ ነው፡፡
እነዚህ ነገሮች እየተለመዱ ሲሄዱ መደበኞቹ አጠቃቀሞች ስህተት ሊመስሉ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ታዳጊ በተደጋጋሚ ‹‹እመጣለው›› የሚል ቃል ከሆነ የሚያነብና የሚሰማው ‹‹እመጣለሁ›› የሚል ቃል ቢያገኝ ስህተት ሊመስለው ይችላል ማለት ነው፡፡ ‹‹ምን ችግር አለው ይሄኛው ቢለመድና መግባቢያ ቢሆን?›› ይባል ይሆናል፡፡ በጣም ችግር አለው፡፡ አንደኛ ቀደም ያሉ መጻሕፍትን ማንበብ ላይቻል ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ በጣም ስህተት ስለሆኑ የትርጉም ለውጥ ሁሉ ያመጣሉ፡፡ በቋንቋ ምሁራን ከተጠናው የሰዋሰው ህግ ውጭ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ለምሳሌ፡- ‹‹በላችሁ›› በሚለው ዓረፍተ ነገር(ቃል) ውስጥ የዓረፍተ ነገሩ ባለቤት ‹‹እናንተ›› የሚለው ነው፡፡ አሁን ፌስቡክ ባበላሸው የቋንቋ አጠቃቀም ስንሄድ ግን ‹‹በላችሁ›› ለማለት ‹‹በላችው›› ተብሎ ይጻፋል? እዚህ ላይ እንግዲህ የዓረፍተ ነገሩ ባለቤት ማነው? ‹‹እናንተ›› ወይስ ‹‹እሷ››? ተመልከቱ እንግዲህ የተፈጠረውን ስህተት! ‹‹እናንተ›› የሚለውና ‹‹እሷ›› የሚለው ተውላጠ ስም ተምታታ ማለት ነው፡፡ ሁለቱ ተውላጠ ስሞች ምንም የማይገናኙ ናቸው፡፡ ‹‹እናንተ›› ሁለተኛ መደብ ብዙ ቁጥር ሲሆን ‹‹እሷ›› የሚለው ደግሞ ሦስተኛ መደብ ነጠላ ቁጥር ነው፡፡
እነዚህ ነገሮች ለጊዜው እንደ ቀላል ይመስሉን ይሆናል፤ ዳሩ ግን ቀስበቀስ ብዙ ጥፋት እያመጡ ነው፡፡ ደጋግሜ እንዳልኩት በዋናዎቹ የመገናኛ ብዙኃንም እንደ ትክክል ተወስደው አገልግሎት ላይ እየዋሉ ነው፡፡ ይሄ ጋዜጠኛ መጽሐፍ እንኳን ቢጽፍ በዚህ ቋንቋ ነው ማለት ነው የሚጠቀመው፡፡
ሌላው ፌስቡክ በቋንቋ ላይ እያደረሰው ያለው ጥፋት ደግሞ የሥርዓተ ነጥብ አጠቃቀም ነው፡፡ ሥርዓተ ነጥብ በአንድ ቋንቋ ውስጥ ትልቅ ሚና እንዳለው ግልጽ ነው፡፡ የትኛውም ቋንቋ የራሱ የሆነ የሥርዓተ ነጥብ አጠቃቀም ሥርዓት አለው፡፡ ብዙ ቋንቋዎች በጋራ የሚጠቀሟቸው የሥርዓተ ነጥብ አይነቶች ቢኖሩም አንዳንዶቹ ደግሞ የራሳቸው ሥርዓተ ነጥብ ያላቸው አሉ፡፡ በመገናኛ ብዙኃን በስፋት አገልግሎት ላይ እየዋለ ያለው የአማርኛ ቋንቋ የራሱ የፊደል ገበታ ያለውና በአፍሪካ ብቸኛ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገለጽ የቆየ ነው፡፡ ይህ ቋንቋችን የራሱ የሆነ የሥርዓተ ነጥብ አጠቃቀምም ያለው ነው፡፡ አማርኛ ከሌሎች ቋንቋዎች ጋር በጋራ የሚጠቀማቸው የሥርዓተ ነጥብ አይነቶችም ቢኖሩም የራሱ ብቻ የሆኑም አሉ፡፡
ፌስቡክ ላይ የሚታየው ግን እንኳንስ የራሱን የሚጠቀሙበትን ቋንቋ የየትኛውንም ቋንቋ የሥርዓተ ነጥብ አጠቃቀም ህግ ያልተከተለ ነው፡፡ ሥርዓተ ነጥብን ያለ አግባብ መጠቀም ደግሞ የትርጉም ለውጥ ሁሉ ያመጣል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ታዳጊዎች ሁሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ያለምንም አገልግሎት በቃላት መካከል ውስጥ የተደረተን ሥርዓተ ነጥብ ሲያዩ ትክክለኛ አገልግሎቱ እንደዚያው ሊመስላቸው ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ጭራሽ መሆን የማይገባውን ሥርዓተ ነጥብ ሁሉ ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩልም አገልግሎት ላይ ካለመዋላቸው የተነሳ የሌሉ የሚመስሉ ሥርዓተ ነጥቦችን ይረሷቸው ይሆናል፡
ለምሳሌ፡- እንደ ድርብ ሰረዝ(፤)፣ ነጠላ ሰረዝ(፣) ሁለት ነጥብ ከሰረዝ(፡-) አቆልቋይ ወይም እዝባር(/)፣ ሁለት ነጥብ(፡) እና የመሳሰሉት ፌስቡክ ላይ አግልግሎት ላይ ሲውሉ አይታይም፡፡ የእነዚህን ሥርዓተ ነጥቦች አገልግሎት ቢጠየቅ ብዙ ሰው ግራ ሊጋባ ይችላል፡፡
ከሰዋሰውና ከሥርዓተ ነጥብ ውጭ ፌስቡክ የአማርኛ ቃላትንም እያጠፋ ነው፡፡ ይሄ እየቆየ ሲሄድ ጭራሽ ያለመግባባት ደረጃ ላይ እንዳያደርሰን፡፡ ቆየት ያሉ መጽሐፍትን ማንበብ ችግር ይሆናል ማለት ነው፡፡
አንድ የዩኒቨርሲቲ ምሁር በአንድ ወቅት ሲያወሩ እንደሰማሁት ‹‹ህ››ን በ‹‹ክ›› እየተኩ በመጠቀም ‹‹በላክ፣ ጠጣክ፣ መጣክ…›› የሚሉ ሰዎች የእንግሊዘኛ ተናጋሪ ለመምሰል የሚያደርጉት እንደሆነ ተናግረው ታዳሚውን ፈገግ አሰኝተውት ነበር፡፡ ቆይ ግን አንድ የእንግሊዘኛ ዓረፍተ ነገር ማንበብ የማይችል ሁሉ ‹‹ ክ›› ስላለ ብቻ ፈረንጅ የሚሆን መስሎት ይሆን?
ለቋንቋና ባህል መበረዝ ብዙ ጊዜ ቴክኖሎጂ ተጠያቂ ሲደረግ ይሰማል፡፡ አንድ የቋንቋና ስነ ጽሑፍ ተመራማሪ በዚህ ጉዳይ ላይ በአንድ ወቅት ቃለ መጠይቅ አድርጌላቸው ነበር፡፡ እርሳቸው የነገሩኝ እንዲያውም ቴክኖሎጂ የበለጠ እንዲተዋወቅ የሚያደርግ፣ ለማስተካከል የሚያግዝና የበለጠ አመቺ እንደሆነ ነበር የነገሩኝ፡፡ የእርሳቸው ሀሳብ ልክ መሆኑን ደግሞ ጥፋት ቢኖርበትም ፌስቡክ ራሱ አሳይቶናል፡፡ ብዙ አባባሎችን፣ የፈጠራ ሥራዎችን፣ ቀልዶችን፣… አይተንበታል፡፡ አሁን እየደረሰ ላለው የቋንቋ አጠቃቀም መበላሸት ፌስቡክ በራሱ ያመጣው ሳይሆን ተጠቃሚው ያመጣው ነው፡፡

ዋለልኝ አየለ

Published in መዝናኛ

ሁሉም ነገር ለበጎ እንደሆነ ያምናል። ፈጣሪ የሰጠውን መክሊት በጸጋ የተቀበለ ሰው ፈጣሪው አንዳች ያጎደለበት እንደማይኖር ይናገራል። ሁልጊዜም አመስጋኝ ነው። ካልተደረገለት ይልቅ የተደረገለት ትልቅ እንደሆነ ያምናል። ተስፈኛም ነው። ነገ ከዛሬ በእጅጉ የተሻለ እንደሚሆን ቅንጣት ያህል አይጠራጠርም። ስለ ነገ በመጨነቅ የዛሬ ደስታውን ማበላሸትም አይፈልግም። በምክንያት ለጥበብ እንደተፈጠረ ያምናልም። ሕይወቱም ሆነ ሞቱ ከጥበብ ጋር እንዲሆን እድሜልኩን ይጸልያል። ለጸሎቱም ምላሽ በማግኘቱ ያሳለፋቸውን አስቸጋሪ ጊዜያት የሚያስረሳውን ጥበብ የሠጠውን ፈጣሪ አብዝቶ ያመሰግናል። የዕለተ ሰንበት የህይወት እንዲህናት እንግዳችን ሰዓሊ ዮሴፍ በቀለ።
በእርግጥ ሕይወት እንዲህ ናት፤ ሕይወት ፈርጀ ብዙ ገጽታ አላት። ህይወት በስዕል ትመሰላለች በብርሃንና በጥላም እንዲሁ። አንድ ጊዜ ስታነሳ ሌላ ጊዜ ደግሞ ትጥላለች፤ ለአንዱ የተትረፈረፈ ሀብት ሰጥታ ጤናውን ታቀውስበታለች። ሌላውን ደግሞ ከሀብቱ ነስታ ህይወቱን ለፍቶና ማስኖ የሚመራበትን ጤናና ጉልበት ትቸረዋለች። ሕይወት በፈተናም የተሞላች ናት፡፡ ብዙዎች ፈተናውን መቋቋም ተስኗቸው ሲንበረከኩ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ጥቂቶች ደግሞ ከፊታቸው የተጋረጠባቸውን የህይወት ፈተና መቋቋም የሚችሉበት ምሥጢር ተችረው ይፈጠራሉና ያልፉታል፡፡
የህይወት ዋጋው ስንት ነው? የሚል ጥያቄ ቢነሳ የሁላችንም መልስ እብዛም የሚራራቅ አይሆንም፡፡ ለሰውነት ክፍላችን ዋጋ ተምኑለት ብንባልም እንዲሁ ቆጥረን የማንጨርሰውን ዋጋ ልንተምን እንደምንችል አያጠያይቅም፡፡ የትኛውን የአካል ክፍላችንን ከየትኛው ማበላለጥ እንደምንችል መቸገራችንም አይቀርም፡፡
«ጫማ የለኝም ብለህ አትዘን እግር የሌለው አለና» የሚለውን አባባል ከሰማነው ረጅም ጊዜያት ተቆጥረው ሊሆን ይችላል። እግር የሌለው ግን ደግሞ ብሩህ ልብ የተቸረው እንዳለ ስናስብ ካጣናው ይልቅ የተሰጠን ብዙ መሆኑን እንረዳለን። አይነስውር ስናይ ልባችን የሚያዝነው ዓይናቸው በጨለማ ቢታጠርም ልባቸው በብርሃን የሚንቦገቦግ መሆኑን ስላልተረዳን ላቸው ሊሆን ይችላል። ሁሉም አካላዊ ጉዳቶች በልባዊ ብቃቶች የተሸፈኑ እንደሚሆኑ የበርካታ አካል ጉዳተኞች ታሪክ ያስረዳናል፡፡
የዮሴፍ በቀለ የአካል ጉዳት የተለየ ቢሆንም እርሱም ልብ ውስጥ ምንም ጉዳት የለምና ከጉዳት አልባዎቹ በተሻለ በልቡ ውስጥ የበዛ እውቀትና ማስተዋል ይገኛል። የአካሉ መጎዳት ወደሚፈልግበት ለመድረስ ጥቂት ድጋፍ ቢፈልግም የሚፈለገውን ከማድረግ ግን አልታገደም።
ከቄስ ሰፈር አስከ ካዛንችስ
ዮሴፍ በቀለ በ1964ዓ.ም አዲስ አበባ ኡራኤል 35 ቀበሌ በተለምዶ ‹‹ቄስ ሰፈር››እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው ወደዚች ምድር የተቀላቀለው። እስከ ስምንት ዓመቱ ድረስ እዚያው የተወለደበት ኡራኤል አካባቢ አድጓል። ቤሰቦቹ ወደ ካዛንችስ የመኖሪያ አካባቢያቸውን በመቀየራቸው እስካሁን ድረስ ኑሮውን በዚሁ አድርጓል። ለዚህም ነው ዮሴፍ ‹‹ኑሮዬንም ሆነ ሞቴን ካዛንችስ ላይ ያድርገው›› የሚለው።
ዮሴፍ ከአካል ጉዳት ጋር ነው የተወለደው። እንደ እድሜ እኩዮቹ ሮጦ አልተጫወተም፤የአካል ጉዳቱ መሮጥ ቀርቶበት ቁሞ መራመድ እንኳ አላስቻለውም። መላ ሰውነቱ አይንቀሳቀስም። ሁሉንም ተፈጥሯዊ እንቅስቃሴዎቹን እና ተፈጥሯዊ ኡደቶቹን በሰው ድጋፍ ነው ያሳለፈው። እናቱ የሱን ህይወት ለማስተካከል ያልገቡበት ጉድጓድ፣ ያልወጡት ተራራ፤ ያልተማጸኑት ታቦት፣ያላስገቡት ስዕለት የለም። በህክምና ሲሰለቻቸው ወደ ፀበል በማመላለስ የእናትነት ኃላፊነት ከሚጠይቀው በላይ መስዋዕትነት ከፍለዋል።
የእምነት አባቶች ዘንድ ፀበል በመመላለስ የሚታወቁት እናቱ የልጃቸው ችግር በተፈጥሮ የመጣ በመሆኑ እንዳይደክሙ ቢመክሯቸውም፤ እርሳቸው ግን ሳይሰለቹ አዲስ ፀበል ወጣ በተባሉት ቦታዎች ሁሉ ይጓዛሉ። መመላለሳቸው በከንቱ አልቀረምና በህፃንነቱ ከነበረው የከፋ ጉዳት የተወሰኑ መሻሻሎች ታዩ። ዮሴፍም ቢያንስ ቆሞ ለመሄድ ያበቃው የቅዱስ ኡራኤል ፀበል መሆኑንን ምስክርነቱን ይሰጣል።
ዮሴፍ በችግረኛ ቤተሰብ ውስጥ ያደገ ነው። አባቱ 1883 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ የችግሩ መጠን እንደከፋ ያስታውሳል። ለቤተሰቡ አራተኛ ልጅ የሆነው ዮሴፍ ኑሯቸው ከእጅ ወደአፍ የሆነው የቤተሰቡን ሕይወት ለመደገፍ በየአብያተክርስቲያኑና በየመስጊዱ የመለመን ግዴታ ወድቆበታል። እናቱ ህይወቱን በልመና መግፋት እንደሌለበት በማመናቸው ትምህርት ቤት ለማስገባት ሞከሩ። ግን ያለበት ተፈጥራዊ ጉዳት ለመማር አስቸጋሪ በመሆኑ ሊገፋበት አልቻለም። ወደ ቄስ ትምህርት ቤት በመሄድ ከሀሁ እሰከ ዳዊት ድረሰ ያሉትን ትምህርቶች በሚገባ ተከታተለ። እግሩ እየጠነከረለት ሲመጣም መሰረተ ትምህርት ገብቶ ማንበብና መጻፍን በሚገባ ለየ።
የእግር ጣት
ዮሴፍ አሰር ዓመት እስኪሆነው ድረስ ቁሞ መራመድ አይችልም ነበር። በጸበል ብዛት እግሩ መራመድ ቢችልም ጫማ ለማድረግ አስቸጋሪ በመሆኑ ብዙ ጊዜ ይወድቅ እንደነበር ያስታውሳል። «መውደቅና መነሳት ያለ ነው» የሚለው ዮሴፍ፤ ደጋግሞ ቢውድቅም በዚያው መቅረትን ግን አይመርጥም። ልቡ ላይ የተለየ ብርሃንና ተስፋ ስለነበረው የዕድሜ እኩዮቹ በእጃቸው ሲጫወቱ እየተቁለጨለጨ መመልከትን አይፈልገውም። እነርሱ በእጃቸው የሚያደርጉትን ጨዋታ እርሱ በእግሩ እያደረገ ያስደንቃቸው ነበር። በእግሩ ብይ ሲጫዎት በእጃቸው ከሚጫወቱት የተሻለ ያነጣጥር እንደነበር ዛሬ ላይ በ46 ዓመቱ ያስታውሳል።
ከእጁ ይልቅ እግሩ እንደሚያግዘው ባወቀም ጊዜ በቄስ ትምህርት ቤት ያወቃቸውን ፊደላት በእግሩ ወረቀት ላይ በመፃፍ ተለማመደ። ከዚያም ቃላትን አገጣጥሞ እድሜ ልኩን የማይረሳውን ደብዳቤ ለመጀመሪያ ጊዜ ለራሱ ፃፈ። የውስጡን ስሜት ማውጣት በመቻሉ ደግሞ ደስታው ወደር አልነበረውም። ፊደላቱ በእግሩ በሚገባ መፃፉን ሲያረጋግጥ የእግሮቹን ጣቶች ስዕል ለመሳል ተጠቀመባቸው። ስዕሎቹ ከራሱ አልፎ ሌሎቹን ማስደነቅ ሲጀምሩ ደግሞ ይበልጥ በመበረታታት ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ እግሮቹን እንደ እጅ በማንቀሳቀስ የሚፈልገውን ሀሳብ በስዕል ማስፈር ጀመረ።
የስዕል ብቃቱም እየጨመረ በመምጣቱ ክረምቱ አልፎ እንቁጣጣሽ በመጣ ቁጥር የወንድሞቹና የአካባቢው ልጆች የአበባ ስዕሎችን እንዲሰራላቸው ይጎርፉ ጀመር። ይህ ችሎታውን የሚያወጣበት አጋጣሚ መሆኑን በማመኑ ለጠየቁት ሁሉ የሚፈልጉትን አይነት የአበባ ስዕሎች በመሳል ያስደስታቸዋል። «እንቁጣጣሽ» ብለው ከሚያገኙት ገንዘብም ያካፍሉት ነበር። በእግሩ በመሳሉ ጓደኞቹ ቢደነቁበትም እርሱ ግን ከዚያ በላይ ትልቅ ነገር ሊሰራ እንደሚችል ራዕይ ነበረውና አዳዲስ ነገሮችን መሞከሩን አላቆመም ነበር።
የአፍ ጥበብ
ከዕለታት በአንዱ ቀን ቤተሰቡ ሁልጊዜም እንደሚያደርጉት ማታላይ ተሰብስብው ይጫው ታሉ፡፡ በጨዋታው መሃል ለዮሴፍ አንድ የስዕል ሀሳብ ይመጣለታል። ያንን ሀሳብ ወረቀት ላይ ለማስፈር በማሰብ ወረቀትና እርሳስ እንዲያቀርቡለት ጠየቀ፤ ጨዋታ በመያዛቸው ግን የሚሰማው ያጣል። ደጋግሞ ይጠይቃል፡፡ በዚህ መሀል ከጨዋታው በመነጠሏ የተበሳጨችው እህቱ ወረቀትና እርሳስ አምጥታ ጠረጴዛ ላይ አስቀመጠችለት። ከዚህ በፊት በእግሩ ስለሚስል መሬት ላይ ነበር የሚያስቀ ምጡለት፡፡ በመሰልቸት ስሜት ጠረጴዛ ላይ አስቀምጣው መሄዷን የተረዳው ዮሴፍ ግን እርሳሱን እና ወረቀቱን በአፉ አንስቶ ወደ መሬት ለማውረድ ሞከረ እንጂ አልተበሳጨባትም፡፡
«ሳይደግስ አይጣላም» እንዲሉ መጀመሪያ ያነሳውን እርሳስ በአፉ እንደያዘው እዛው ጠረጴዛው ላይ ለመፃፍ ሲሞክር ተሳካለት። በዛው ዕለት እራሱን እያለማመደ በአፉ መፃፍ ጀመረ። በዛች አጋጣሚ የተጀመረው በአፍ መጻፍና መሳል ብቃት እየጎለበተ መጥቶ ዛሬም ድረስ በአገራችን ብቸኛው በአፉ የሚስል ሰዓሊ ለመሆን አበቃው። ዮሴፍ ‹‹ችግር ብልሃትን ይወልዳል›› በሚለው አባባል ይስማማል። ለአንዱ ችግር ሌላ ብልሃትን መፈለግ ከፈጣሪ የተሰጠው መክሊት እንደሆነም ያምናል። እንደቀልድ በአንድ አጋጣሚ የጀመረው በአፍ የመሳል ጥረት ዛሬ ላይ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በመዘገቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ አድርጎታል። ቀን ያወጣውና እራሱን ለመግለፅ ምክንያት የሆነውን በእግር ጣቶቹ የመፃፍ ክህሎት ዛሬም ድረስ መርሳት ስለማይፈልግ አልፎ አልፎ ይለማመድበታል።
ጥበብን ፍለጋ
በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ሬዲዮ «ብሩህ ተስፋ» በተሰኘ የአካል ጉዳተኞች ፕሮግራም ላይ ሰለ አንዲት አሜሪካዊት ሰዓሊ ዘገባ ያቀርባሉ፡፡ በአፏ መሳል በመቻሏ ዓለም አቀፍ እውቅና ማገኘቷን ያወራሉ፡፡ ሰዓሊዋ የአካል ጉዳት የደረሰባት ከጊዜ በኋላ ቢሆንም የስዕል ጥበብን በአፏ ለመለማመድ ያደረገችውን ጥረት በሚገባ ሲረዳ እርሱም ማድረግ እንደሚችል ለራሱ ቃል ገባ።
የስዕል ትምህርት የሚያገኝበትን ሁኔታ ሲያጠያይቅ አቢሲኒያ የስነ-ጥበብ ትምህርት ቤት የሚባል እንዳለ ተነገረው። በሦስተኛው ቀን ወደ ተቋሙ ሄደ፡፡ በወቅቱ የትምህርት ቤቱን ባለቤት ባያገኛቸውም ሰዓሊ ግርማ አገኘሁ እንግዳወርቅን ስላገኛቸው ለስዕል ስላለው ፍቅርና ጅምር እውቀቱን በትምህርት ማዳበር እንደሚፈልግ ያጫውታቸዋል። ሀሳቡን አድንቀውም የ8ኛና የ10ኛክፍል ያጠናቀቀ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ያስፈልግና ማስረጃውን እንዲያመጣ ይነግሩታል። እርሱ ምንም አይነት የትምህርት ማስረጃ ስላልነበረው አንገቱን አቀርቅሮ ይቀራል። ይሁን እንጂ ህልሙን ለማሳካት በትምህርት ማስረጃ ሰበብ ሊያደናቅፈው እንደማይገባ በማመኑ ተስፋ ቆርጦ ለመመለስ አልፈቀደም፡፡ ይልቁንም በብዙ ልመና ትምህርቱን መማር እንዲችል ተማጸናቸው።
ፍላጎቱንና ተስጥኦውን የሰሙት የትምህርት ቤቱ ባለቤት ወይዘሮ ገነት ከበደ አንድ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠው እንዲማር ፈቀዱለት። «ለጊዜው መማር ትችላለህ፤ ነገር ግን መመረቅ አትችልም›› ተባለ። ዮሴፍ ፍላጎቱ እውቀት እንጂ ወረቀት ባለመሆኑ ይህን ቅድመ ሁኔታ ሳያቅማማ ተቀበለው። ከዛም እርሳስና ወረቀቱን ይዞ ከካዛንችስ ሰባ ደረጃ ናዝሬት ስኩል አካባቢ በሚገኘው የአቢሲኒያ የስነ-ጥበብ ትምህርት ቤት በመመላለስ መማር ጀመረ።
በ1997ዓ.ም ጥቅምት16 ስሙን በተማሪነት መዝገብ ላይ አስመዝግቦ መማር ሲጀምር ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኛቸው ሰዓሊ ወርቁ ማሞን ነበር። እርሳቸውም ከጊዜ በኋላ የአካል ጉዳተኛ በመሆናቸው በአስቸጋሪ ሁኔታዎችን አልፈው ዛሬ ላይ ከፍተኛ እውቅናና ዝናን ያተረፉ መሆናቸውን እየነገሩ እንዲበረታ አደረጉት። የክፍል ተማሪዎቹ በሙሉ የአካል ጉዳት የሌለባቸው በመሆናቸው ከእነርሱ ጋር ተፎካክሮ መማሩ አስቸጋሪ ቢሆንበትም አንድ ጊዜ ልቡን አነሳስቷልና ከእነርሱ እኩል የንድፈ ሃሳቡን ትምህርት አጠናቆ እርሳስና ወረቀትን በአፉ በማገናኘት የተግባር ትምህርቱን መለማመድ ጀመረ፡፡
የእርሳስ ቅብ፤ ጥላና ብርሃን ውስጡ በመራው መንገድ ቀድሞ በቤቱ ተለማምዶት ነበርና ያን ያህል ከባድ አልሆነበትም ነበር። ለሰባት ወራት ያህል ከእርሳስና ከወረቀት ጋር ተጨዋወተ፤ ጭውውቱ ደግሞ ፍሬ ያለው ነበርና የሚያማምሩ የቅብ ስዕሎችን ወደዱለት። በስዕሎቹ እየተበረታታ ቢመጣም በአፍ እርሳስ መቀባቱ እጅግ በጣም ፈትኖት አንደነበር አይዘነጋውም። በተለይም በእርሳስ ቅብ ሲሰራ ጭንቅላቱ በሙሉ ስለሚንቀሳቀስ ህመሙንና ድካሙን ተቋቁሞ ነበር የሚሰራው፡፡ ይህን ችግር የተረዱት አስተማሪው ሰዓሊ ወርቁ የእርሳስ ቅቡን አቋርጦ ወደ ቀለም ቅብ እንዲገባ ቢፈቅዱለትም እርሱ ግን አሻፈረኝ አለ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እኔ አካል ጉዳት ከሌለባቸው በምንም አላንስም የሚል ነበር። እንዳሰበውም ችግሮቹንና ህመሙን ተቋቁሞ ስልጠናውን በሚገባ አጠናቀቀ፡፡
በአንድ ወቅት የትምህርት ቤቱ ባለቤት ወይዘሮ ገነት ወደቢሮ ያስጠሩትና ‹‹አንተ ማስረጃ ባለማቅረብህ እንደማትመረቅ ፈርም›› ይሉታል። ሳያቅማማ ይፈርማል። በሌላ ጊዜ ደግሞ እንዲህ ሆነ፤ ወደ ቢሮ ተጠራ። ‹‹ዛሬ ደግሞ ምን አድርግ ሊሉኝ ነው ወይስ ሊያባርሩኝ›› ብሎ በሰጋበት ወቅት የተነገረው ለማመን ተቸግሮ እንደነበር ያስታውሳል። «አንተ ምንም እንኳን የትምህርት ማስረጃ ባይኖርህም ከሌሎቹ ተማሪዎች የተሻለ ብቃት እንዳለህ በመረዳታችን አሸንፈሃልና እንደማንኛውም ተማሪ እንድትመረቅ ወስነናል»ተባለ። ራስ ሆቴል በድምቀት በተከናወነው የምርቃት ስነ-ስርዓት ላይ ዮሴፍም ጥቁሩን ጉዋን ለብሶ በስዕል ጥበብ ተመረቀ።
ችግር ብልሃትን...
ዮሴፍ ሰዓሊነቱን ወይም የስዕል ብቃቱን በወረቀት አረጋግጧልና የሙያ ማረጋገጫ ቅጽል ጨምረንለት ሰዓሊ ዮሴፍ ለማለት ወደናል፡፡ ሰዓሊ ዮሴፍ ከምርቃት በኋላ የሙሉ ጊዜ ሰዓሊ ለመሆን አልሞ ቢወጣም ነገሮች ሁሉ እንደሚፈልገው አልሆኑለትም። የሚኖረው ከቤተሰቦቹ ጋር በአንዲት ጠባብ ክፍል በመሆኑ ስዕልን መተዳደሪያ አድርጎ ለመስራት አስቸጋሪ ሁኔታ ገጠመው። ስዕል በባህሪው ጸጥታና ሰላምን ይፈልጋል። እንኳን እንደርሱ አይነት የአካል ጉዳት ያላባቸው ሰዎች ይቅርና ጉዳት የሌለባቸውም ቢሆኑ ምቹ የስራ ቦታ ይፈልጋሉ።
ሰዓሊ ዮሴፍ ግን ይህን ለማግኝት ፈፅሞ የማያስበው በመሆኑ የነበረው ብቸኛ አማራጭ ወደተማረበት የስዕል ትምህርት ቤት በመመለስ ሰራዎቹን እዛው ሆኖ እንዲሰራ መጠየቅ ነበር፡፡ ጠየቀ፤ ብቃቱንና ችግሩን የሚያውቁት የትምህርት ቤቱ ባለቤትም አላሳፈሩትም ፈቀዱለት። እስካዛሬ ድረስ፤ ማለትም በትምህርት ወቅት ለአንድ ዓመት ከምረቃ በኋላ ለሰባት ዓመታት በፈለገበት ጊዜ ገብቶ፤ በፈለገበት ጊዜ ወጥቶ የሚሰራበት የስዕል ስቱዲዮው አቢሲኒያ የስነ-ጥበብ ትምህርት ቤት ሆነ።
ዮሴፍ በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ስዕል ለመሳል የሚያደርገውን ጥረት ማየት በራሱ ምንያህል በስዕል ፍቅር እንደወደቀ ያሳብቃል። ነገር ግን ባለችው አንድ ክፍል ውስጥ ከሳጥን ላይ ጠረጴዛ ደርቦባት ለመቆምም ሆነ ለመቀመጥ በማይመች ሁኔታ ለመሳል ጥረት ያደርጋል፡፡ይህ ደግሞ እንኳን የአካል ጉዳት ላለበት ሰው ይቅርና ጉዳት ለሌለበትም የማይመች መሆኑን መረዳት አያስቸግርም።
መስዋዕትነት የተከፈለበት ፍቅር
ሰዓሊ ዮሴፍ ትዳርን የጀመረው ከ20 ዓመት በፊት ነው፡፡ የመጀመሪያ ባለቤቱና የአንድ ልጅ እናቱ አብሮአደግ ፍቅረኛው ነበረች። እንዴት አካል ጉዳተኛ ታገቢያለሽ? ተብላም ብዙ መከራዎችን አብራው አሳልፋለች፡፡ ለእርሱ ስትል ከቤተሰቦቿ እስከመባረር ደርሳለች። የአካል መጎዳት የልብ መጎዳት ባለመሆኑ ፍቅርን እንደማይገድበው ያሳየችበት ወቅት ነበር። ፍቅራቸው የሚያስቀና ለሌሎች አርአያ የሚሆን የፍቅርን ሀያልነት ያሳዩበት ወቅትም ይህ እንደነበር ያስታውሳል።
የቤተሰብ ተፅዕኖ እየከፋ ሲመጣ ቤት ተከራይተው ወጡ። በወቅቱ ሰዓሊ ዮሴፍ ምንም መተዳደሪያ ባይኖረውም ወዳጆቹን ተማምኖ ነበር ቤት ተከራይቶ የወጣው። ካዛንችስ ለዮሴፍ ህልውናው ነበረች፡፡ እየለመነ በሚያገኘው ገንዘብ ነበር ቤተሰቡን የሚያስተዳድርባት። የካዛንችስ ቡና ቤቶች የዮሴፍ ህልውና ስለነበሩ ዛሬም ድረስ ያመሰግናቸዋል። እንደሌሎቹ ቀን እየቆጠረና የመላዕክትን ስም እየጠራ ባይለምንም እጁን ብቻ በማሳየቱ ያዘነ ይሰጠዋል።
በፍቅር የዘለቀው ትዳር በአንዲት ሴት ልጅ ተባረከ። ይሁን እንጂ ባለቤቱ የአራት ወር ልጅ ጥላበት ይችን ዓለም ተሰናበተች። ወቅቱ ለዮሴፍ አስቸጋሪ ነበር። ኑሮን ታግሎ ማለፍ ከፈጣሪ የተሰጠው ፀጋ በመሆኑ ለሦስት ዓመታት ብቻውን ልጁን አሳድጓል። እራሱ በሰው ድጋፍ እየኖረ የአራት ወር ህፃን ማሳደግ ምን ያህል ከባድ ነው? እርሱ ግን ‹‹ሀይልን በሚሰጠኝ ሁሉን እችላለሁ›› እያለ ሁሉንም ችግሮች አልፎ ከሁለተኛ ሚስቱ ጋር በአጋጣሚ ተገናኘ።
መተዛዘን ያበረታው ትዳር
የመጀመሪያ ባለቤቱ ካለፈች በኋላ የሚመገበው ሆቴል ነበር። አዘውትሮ በሚመገብበት ሆቴል እንደልማዱ ተገኝቷል። ምግብ አዞ የሚያጎርሱት ጓደኞቹን በመጠባበቅ ላይ ሳለ ጓደኞቹ የውሃ ሽታ ሆኑ። የነበረው ብቸኛ አማራጭ ምግብና ዮሴፍ መፋጠጥ ብቻ ነው። ርሃብ እየሞረሞረው ከምግብ ጋር የተፋጠጠው ዮሴፍ በሆነው ሁሉ አልተከፋም። እንደውም ወትሮም እንደሚያደርግው በራሱ እየቀለደ ይዝናናበታል። በዚህ መሃል በሁኔታው ያዘነችው የሆቴሉ ምግብ አብሳይ(ሸፍ) ልታጎርሰው ፍቃደኛ ሆነች። መሀል ላይ ባለቤቱ አንድ ልጅ ጥላበት እንደሞተች ሲነግራት ሀዘኗ በእጥፍ ይጨምራል። በማዘን የተጀመረው መቀራረባቸውም ወደ ፍቅር እየተቀየረ ይሄዳል።
በአጋጣሚ በማጉረስ የተዋወቃት የአሁኑዋ ባለቤቱም ፍቅር ልቧ ውስጥ ድንገት ተሰንቅሯልና ልትለየው አልፈቀደችም። ይልቁንም ስራዋን ሁሉ ትታ እርሱን ተከትላ ልትንከባከበው ወደቤቱ ገባች። በአንድ በኩል ልጁን በሌላ በኩል ደግሞ እርሱን እየተንከባከበች በፍቅርና በደስታ እየኖረችም ነው። በትዳራቸውም አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጅ አፍርተዋል። «ፈጣሪ ይመስገን አንድም ቀን ጎደለብን ሳንል በደስታ እንኖራለን» የሚለው ሰዓሊ ዮሴፍ አመስጋኞች የተባረኩ ናቸው እንዲሉ፤ ብዙዎቻችን ሞልቶና ተትረፍርፎልን እንኳ ባጣናት ጥቂት ነገር ስናማርር ሰዓሊ ዮሴፍ ግን በሁሉም ነገር ደስተኛና አመስጋኝን ልብ የተሰጠው መሆኑን ከዚህ መገንዘብ ይቻላል። ባለቤቱ የሆቴል ሙያ ስላላት ልጆቹን ከመንከባከብ ባለፈ የሰርግና የተለያዩ የድግስ ስራዎችን በማከናወን በምታገኘው ገንዘብ ታግዘዋለች። የተሻለና ቋሚ ስራ እንድታገኝም «ሙያዋን የምታውቁ እባካችሁ በእርሷ በኩል አግዙኝ» ይላልም።
ሰዓሊ ዮሴፍ የሦስት ልጆች አባት ሲሆን፤ የመጀመሪያ ልጁ አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኢንጅነሪንግ ተማሪ ነው። ሁለተኛ ልጁ ደግሞ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፤ ሶስተኛ ልጁ ኬጂ ትማራለች። ሁልጊዜም በፈጣሪ እምነት ስላለው በነገሮች ሁሉ ፈጣሪ ቤተሰቡን ሁሉ በመልካም እንደደገፈለት ያምናል። ለደቂቃ በህይወቱ ተማሮ አያውቅም። ልጆቹን በአግባቡ እንዲማሩ የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡ በእርሱ ያጣውን በልጆቹ መካስ ስለሚፈልግ በትምህርት ራሳቸውን እንዲችሉም ያግዛቸዋል።
የንባብ ፍቅር
ሰዓሊ ዮሴፍ ወደ ስዕል ጥበብ ነፍሱ ትሳብ እንጂ ከምንም ነገር በላይ የሚያስደስተውና የበዛውን ጊዜ የሚያሳልፈው መፅሀፍትን በማንበብ ነው። ምንም አይነት የተፃፈ ነገር ለዮሴፍ ዋጋው የከበረ ነው። የሚነበብ ነገር ካገኘ ደግሞ ደጋግሞ በማንበብ እውቀቱን እንዳዳበረበት ይናገራል። ‹‹ስዕል ለእኔ ትልቅ የመንፈስ እርካታ ነው። በቀን አንድ መስመር እንኳን ካላሰመርኩ ይጨንቀኛል›› የሚለው ሰዓሊ ዮሴፍ በአምባቢነቱም ብዙ አትርፏል። ለህትመት የበቁ መፅሀፍትን ሁሉ ባገኘው አጋጣሚ በመግዛት ለማንበብ ጥረት ያደርጋል። የስዕል ሀሳቦች የሚመጡለትም የሚያነባቸው መፅሀፍት ናቸው።
መፅሀፍ ማንብብ ለብዙዎቻችን መዝናኛ ቢሆንም ለሰዓሊ ዮሴፍ ግን አስቸጋሪ ስራም ጭምር ነው። መፅሀፍ ለማንበብ ምቹ ቦታ ይፈልጋል። መጽሀፉን ለመግለጥ የሚጠቀመው ምላሹን እና ከንፈሮቹን ሲሆን፤ የተገለጠውን ገፅ ለማቆየት ደግሞ ተጭኖ የሚይዝለት ነገር ይፈልጋል። አሁን ላይ ተንቀሳቃሽ ስልኩን ቢጠቀምም በፊት ግን በችግር ውስጥ ሆኖ ነበር በርካታ መፅሀፍትን ያነበበው። ጋዜጦችና መፅሄቶች አያልፉትም። ወንጀልነክ ዘገባዎች ይበልጥ ይመስጡታል። እስከ ዛሬ ካነበባቸው መፅሀፍት ታሪካቸውን የማይዘነጋቸው በርካቶች ቢሆኑም የሰመመንን ያህል በውስጡ የቀረ እንደሌለ ይናገራል። ሰዓሊ ዮሴፍ መፅሀፍ ተውሶ ማንበብ አይወድም። ‹‹ማንበብ ሙሉ ሰው እንደሚያደርግ›› ያመነው ከሰላሳ ዓመት በፊት በመሆኑ ለመፅሀፍ የሚያወጣው ገንዘብ አይቆጨውም። ማህበራዊ ግንኙነቱ ሰፊነው።(ከኔም ጋር የተዋወቅነው በማህበራዊ ሚዲያ ነው) በተለይም በፌስቡክ ላይ ይሳተፋል። ከአድናቂዎቹና ወዳጆቹ ጋርም በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ይወያያል። የስዕል ስራዎቹንም ፌስቡክ ላይ በማስቀመጥ አስተያየት ይቀበላል። እንደዛም ሆኖ ፌስቡክ መጠቀም ለሰዓሊ ዮሴፍ ቀላል አይደለም። በከንፈሮቹ፣ በምላሱና በጭንቅላቱ ጭምር መጠቀም ይኖርበታል። በአካል ጉዳተኛነቱ ይቀልዳል። ይዝናናል፤ ወዳጆቹንም ያዝናናል።
የአውደ ርዕይ ተሳትፎ
በስዕል ስራዎቹ የሚመርጣቸው ውሃ ቀለሞች ሲሆኑ፤ መልክዓምድራዊ አቀማመጥና የከተማ ገፅታዎችን መሳል ይመርጣል። ከከተማ ገፅታዎች ውስጥ ካዛንችስ አካባቢ የነበሩትን የጣሊያን ህንፃዎች በፎቶ አስነስቶ ስሏቸዋል። እስካሁን የተወሰኑ የስዕል አውደ ርዕዮች ላይ ተሳትፏል። በአካል ጉዳተኞች በተዘጋጁ አቢሲኒያ የስነ-ጥበብ ትምህርት ቤት ባዘጋጃቸው፣ ብሄራዊ ሙዚየም በተካሄዱ የስዕለ አውደ ርዕዮች ላይ ተሳትፏል።
በተለይም በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በአካል ጉዳተኞች በተካሄደው የስዕል አውደ ርዕይ ላይ በርካታ አንጋፋ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በመጎብኘታቸው ስራውን በማድነቅ እንዳበረታቱትና ለበለጠ ሥራ እንዳነሳሱት ይናገራል። «እኔ አፍ መብያ እንጂ መስሪያ መሆኑን ያውኩበት ሰው» የሚለውን አስተያየት በአድናቆት ተቀብሎታል። ‹‹ስዕል ዝናና ቲፎዞ ይፈልጋል›› የሚለው ሰዓሊ ዮሴፍ በተለያዩ አጋጣሚ ለሚዲያ ቢቀርብም አድናቆትን ከመለገስ ባለፈ ቀርቦ የደገፈው እንደሌለ ያስረዳል።
ሆቴሎችም ለመርዳት ያህል ስዕሎቹን በመግዛት ቢያግዙት ለበለጠ ሥራ እንደሚያነሳሳውም ይናገራል። በተለይ ሆቴሎች በካዛንችስ አካባቢ እየተስፋፉ በመሆኑ ቢያንስ አንዳንድ ስዕል ቢገዙ ወይም ደግሞ አንድ ክፍል የስዕል ስቱዲዮ ቢለግሱት የበለጠ ብቃቱን አውጥቶ ለመስራት እንደሚያስችለውም ይገልጻል። ‹‹መንግሥት ለሁሉም የቆመ ነው፡፡ በመሆኑም እኔም እንደዜጋ የመስራት እድል ተመቻችቶልኝ ሀገሬን እንዳስጠራ ቢያግዘኝ መልካም ነው። ሌሎች ብቃት ኖሯቸው ያልወጡ ብዙ አካል ጉዳተኞች ስለሚኖሩ ሊደግፈን ይገባል። ወጣቶች ሥራ እንዲፈጥሩ ብዙ ጥረት እየተደረገ ነው ለዛም ምሳሌ መሆን ስለምችል የእኔን ጥረት አይተው ብዙ ወጣቶች ሊነሳሱ ይችላሉና ለእኔ የስዕል መስሪያ ቦታ ቢተባበሩኝ ክብሩ የጋራ ይሆናል›› መልዕክቱ ነው።
ምስጋና
የሰዓሊ ዮሴፍ ስዕሎች ከሀገር ቤት አልፈው በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በኤሽያ ይገኛሉ። እንግሊዝ፣ ካናዳ ደቡብ ኮሪያ ስራዎችን ገዝተው ከወሰዱት ውስጥ ይጠቀሳሉ። በተለይ አንዲት ደቡብ ኮሪያዊት የራሷን ምስል (ፖርትሬት ስዕል) አሰርታ መወሰዷ ለእርሱ ያላት አድናቆት የገለፀችበት እንደሆነ ያምናል። ‹‹የውጮቹ ሰዎች አድንቀው ሲያበረታቱኝ በአገር ቤት የሚያግዘኝ ሰው ማጣት የለብኝም›› የሚለው እንግዳችን ለመጀመሪያ ጊዜ ስዕሎቹን የገዙት ሰዎች አበርትተውታልና ያመሰግናል። እሰካሁን ወይም 13 ዓመታት አቢሲኒያ የስነ-ጥበብ ትምህርት ቤት ባለቤት እየደገፈችው በመሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያመሰግንለት በአክብሮት ይጠይቃል።
በስዕል ትምህርት ቤት ቆይታው የሰዓሊ ወርቁ ጎሹ ልጅ አባቷን ልታግዝ ስትመጣ ትረዳው ስለነበር። የእርሷን ውለታ ዛሬም እንደማይዘነጋው ይናገራል። ሰዓሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታን፣ አስተማሪዎቹን ሰዓሊ ወርቁ ማሞ፣ ሰዓሊ ግርማ ሰቦቃ፣ ሰዓሊ ግርማ አገኘሁ እንግዳወርቅ፣ ሰዓሊ ደረጀ ከበደና ሌሎቹንም ያደንቃል፤ ያመሰግናልም። እንዲሁም ከልጅነት እስከ እውቀት ድረስ ከጎኑ ያልተለዩትን ቤተሰቦቹንና የካዛንችስ አካባቢ ነዋሪዎችን ፈጣሪ ብድሩን እንዲከፍላቸው ይመኛል።
«ነብይ በሀገሩ...»
ሰዓሊ ዮሴፍ ብቸኛ በአፉ የሚስል የጥበብ ሰው ነው፡፡ 100 ሚሊዮን ህዝብ ባለባት ሀገር ውስጥ በአፉ የሚስል አንድ ሰው ቢኖር እርሱም ዮሴፍ ነው። ይህ ራሱን በራሱ አስተምሮ ዛሬ ላይ የደረሰን የጥበብ ሰው ሀገሩ 3በ3 የሆነ የመሳያ ቦታ ነፈገችው ቢባል ለማመን የሚከብድ እውነታ ነው፡፡ በርካታ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በተለይም በአካል ጉዳተኞች ላይ ትኩረታቸውን አድርገው የሚሰሩ ድርጅቶች፤ ጥበብ ወዳድ ባለሀብቶች እንዲሁም በጥበብ ላይ የሚሰሩ የመንግስት ድርጅቶች ባሉበት ሀገር ይህን ችግር መስማት ያሳፍራልና ሀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የብዙዎች ሀሳብ ነው።
‹‹ስዕሌን የውስጥ ስሜቴን አውጥቸባታለሁ፤ ህይወቴንም መርቸባታለሁ›› ብሎ የማያስበው ሰዓሊ ዮሴፍ፤ የቦታ እጥረት ፈተና እንደሆነበት ይናገራል። « የእኔ ህልም በአፏ እየሳለች ሀገሯን እንዳስጠራችው አሜሪካዊት ሰዓሊ ሀገሬን ማስጠራት ነው። እኔ እንደሆንኩ በችግር ተፈትኜ እራሴን ዛሬ ላይ አድርሻለሁ፡፡ ወደፊትም ራሴን እና ቤተሰቦቼን ለማስተዳደር አልቸግር ይሆናል። ነገር ግን የእኔ ህልም ከዚህ በላይ የገዘፈ ነው። ከምንም በላይ ሀገሬንና ህዝቤን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስጠራት እፈልጋለሁ። ለዚህ ደግሞ መንግሥትና ባለሀብቶች ትንሽ ድጋፍ እንዲያደረጉልኝ እፈልጋልሁ። ትንሽ የመስሪያ ስቱዲዮ ብቻ ባገኝ ህልሜን አሳካለሁ» ይላል ሰዓሊ ዮሴፍ። ወደፊት ፈጣሪ ፈቅዶ ባለሀብቶችም ሆነ መንግሥት ደግፈውት የተመቻቸ ቦታ አግኝቶ ራሱንም ሆነ ሀገሩን የሚያስጠራ ሥራ መስራት ይፈልጋል። በእርግጥም ህይወት እንዲህ ናት! መልካም ዕለተ ሰንበት!

ዳንኤል ወልደኪዳን

Published in ማህበራዊ

ኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለ17 ቀናት የሁኔታዎች ግምገማ አድርጎ ውሳኔዎችን ማስተላለፉ ይታወሳል። ችግሮቼም እነዚህ ናቸው ሲል ለህብረተሰቡ ይፋ አድርጓል። ይህንንም ተከትሎ ችግሮቹን ለመፍታት የተለያዩ ተግባራትን በመከወን ላይ ይገኛል። ከእነዚህ መካከልም በየደረጃው የሚደረጉት የውይይት መድረኮች በዋናነት ይጠቀሳሉ።
ሰሞኑን የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ አራተኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተው የመወያያ አጀንዳዎችና አቅጣጫዎች ተሰጥቶበታል። በተለይም ድርጅቱ የለያቸውን ጉዳዮች በተመለከተ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።
በወቅቱ እንደተባለው፤ ዴሞክራሲው ሲሰፋ፣ ልማት ሲበራከት በርካታ ጥያቄዎች ይነሳሉ። ይህ ደግሞ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲጋለጡ አድርጓል። በተለይም በአመራር ድክመትና በሙስና እንዲሁም ብልሹ አሰራሮች ምክንያት ችግሮቹ መስፋታቸው ይበልጥ ሊሰራበት እንደሚገባም ተጠቁሟል። የህዝቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማስፋት፣ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ የግልፅነትና የተጠያቂነት አሰራርን ለማንገስና ውጤታማና ቀልጣፋ አስተዳደር ለመገንባት የተደረጉ ጥረቶችን ፍሬያማ እንዳይሆኑ ያደረገው ይህ አሰራር መሆኑ ተነስቷል። በተለይ ወጣቱ ትውልድ አገር ተረካቢ እንደመሆኑ መጠን በየደረጃው በቅን ልቦናና መንግሥታዊ መመሪያዎችን በተከተለ አኳኋን ህዝቡን ማገልገል እንዳለባቸው ነው የተገለጸው።
ተሳታፊና ተጠቃሚነት የሚያረጋገጥበት ዕድል እንዳይቀንስም መታገል እንደሚገባ ተጠቁሟል። ከፍተኛ የሕዝብ ምሬት የሚፈጠርበት፣ የህግ የበላይነት የማስፈን ድክመት የሚታይበት፣ በሙስናም ሆነ በሌሎች ጥፋቶች ውስጥ የተዘፈቁ ግለሰቦችን በወቅቱ ህጋዊና አስተማሪ በሆነ መንገድ መጠየቅ ያልተቻለበት መንገድ የሰፋ ስለነበር እስከአሁን በድርጅቱ ላይ በርካታ ችግሮች እንዲጋረጡበት አድርጓል። አሁን ግን ይህ ችግር ይበልጥ እንዳይሰፋ ወጣቱ በችግሩ ዙሪያ ርብርብ አድርጎ ሊፈታው እንደሚገባም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።
የኢህአዴግ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደተናገሩት፤ ዜጎች በህገመንግስቱ ዋስትና አግኝተው መብቶቻቸው እንዲረጋገጥላቸው የሆነው ኢህአዴግ እስካሁን ታግሎ ባመጣቸው ምቹ ሁኔታዎች ነው። ይሁን እንጂ የህዝብና የአገር ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በተነደፉት ፕሮጀክቶች ዙሪያ በሚታዩ የአፈፃፀምና የስነ-ምግባር ችግሮች ሳቢያ አስተማማኝና ውጤታማ በሆነ መንገድ የማረምና የማስተካከል ሁኔታ ወጥነት ያለው ባለመሆኑ ቅሬታዎች እንዲሰፉ ሆኗል። ስለዚህ ወጣቱ አገሪቱ በሁሉም መስክ ተወዳዳሪና ህዝቦችን ተጠቃሚነት ሊያደርጉ የሚገባቸው ፕሮጀክቶች ላይ በአግባቡ በመሳተፍ ችግሮችን ሊታገል ይገበዋል። ህዝብና አገርን ያልተገባ ዋጋ የሚያስከፍሉ አካላትን በጉልበትም ሆነ በመስራት የሚያሸንፈው እርሱ ነውናም አሰራሮችን ማዘመን ላይ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ገለጻ፤ የመልካም አስተዳደር ችግር በተግባር ማቃለል ሲገባ ባጉል ተስፋና በባዶ ቃልኪዳን የመሸንገል ህዝበኛ አዝማሚያዎች በጥብቅ መመከት የሚገባው ወጣቱ ነው፤ የአሰራሮችን ብልሹነትም ማመላከት ይኖርበታል፤ ማህበረሰቡን በአንድ ጀንበር ማርካት አይቻልምናም ዛሬ ላይ ኢህአዴግ በብዙ ፈተና ውስጥ እንዲገባ የሆነውም የህዝቡ ጥያቄ በመበራከቱ ስለሆነ በዘርፉ ለሚደረገው ትግል ወጣቱ መፍቻ መንገዱን በማመቻቸት ሊሳተፍ ያስፈልጋል። የወጣቱ ችግር ተፈታ ማለት እንደሆነ ተገንዝቦ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል።
ኢህአዴግ በትግል የማሸነፍን ራዕይ አንግቦ የሚጓዝ ድርጅት ነው፤ እጅም አይሰጥም። ለዚህ ደግሞ ማሳያ የሚሆነው ችግሩን አይቶ ራሱን ለማሻሻል መዘጋጀቱ መሆኑን የሚጠቁሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ወጣቱ ሊግ የኢህአዴግ ህብረት ማሳያ ነው፤ በዚህ ሊግ ውስጥ የታቀፈው ወጣት ለእኩል ተጠቃሚነት የተሻለ አስተዋጽኦ ያደርጋል፤ አሁን የተያዘውን የህዳሴ ጉዞ ለማጠናከርና ከግብ ለማድረስ ሁነኛ ሚና ይጫወታል። በተለይም የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ በአገሪቱ ዋና ከተማ ላይ የሚገኝና ህብረ ብሔራዊነት የሚታይበት በመሆኑ በለውጡ ላይ ቢሳተፍ ውጤታማ እንደሚሆን ይገልጻሉ።
በአንድነት የመጓዝና የመስራት እንዲሁም በአንድነት የመታገልን ምንነት ማሳያው ይህ ሊግ ነው። ሁሉ ነገር በአንድ ትንፋሽ የሚጓዝበት፣ነጻ አመለካከት የሚራመድበትና በአንድነት ተግባራት የሚከወንበት ሊሆን ይገባዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፤ ከዚህ ሊግ የኢህአዴግ አመራር ወጥነት ያለው አሰራርን ይማርበታል፤ ነገር ግን በውስጡ ህብረ ብሔራዊ መሆኑን፣ ምን አንድምታ እንዳለውና ማንነቱ በምን መልኩ እየተለካ እንዳለ ማሳየት ይጠበቅበታል። ለዚህም ጥገኛ አመለካከቶችን የሚያስወግድበት የሊግ አመሰራረት ስላለው ሊጠቀምበት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።
«አሁን ያለንበት ምዕራፍ ሁለት ጉዳዮች የሚታዩበትና መሳ ለመሳ እየሄዱ ያለበት ነው። አንደኛው ለ26 ዓመታት በተሰሩ ስራዎች ፈጣን እድገት የተመዘገበበት ሲሆን፤ ተከታታይ የሆነ እድገት የመጣበት መሆኑም ግልጽ ነው። ህዝቡም ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ ይገኛል። ይሁንና በሌላኛው ጎራ ሲታይ ፈታኝ ችግሮች ያጋጠሙበት ጊዜ መሆኑን መጠቆም ይቻላል» ሲሉ የሚያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ «ህዝባችን የልማት፣ የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር ጥማት ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍ ያለበት በመሆኑ የህዝቡን ጥማት ለማርካት ከፍተኛ ትግል ማካሄድ የሚገባን ጊዜ ነው። ነገር ግን ኢህአዴግ በውስጡ በተፈጠሩ ብልሹ አሰራሮች ምክንያት ይህንን የህዝብ ፍላጎት በሚፈለገው ደረጃ አላረካም። ስለዚህም ይህ ጉባኤ እነዚህን ሁለት ተቃራኒ ጉዳዮች በማጣጣም ድርጅታችን ምንም ያህል ችግሮች የተደራረቡበት ቢሆንም በትግሉ ማሸነፍ እንደሚችል የምታሳዩበት ሊሆን ይገባል።» ይላሉ።
«ኢህአዴግ ትግሉን ከጀመረበት ጀምሮ የሚገነባውን ታዳጊ የካፒታሊስት ስርዓት በሽብር ወቅት ያለ መሆኑን በመገንዘብ ወደ ዳበረ ካፒታሊስት ስርዓት እስኪሸጋገር ድረስ የሚያዳክመውን የስርዓቱ አደጋ በተሀድሶው መመለስ ይገባል» ብሎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ስለሆነም እናንተም የዚህ ድርጅት አንድ አካል በመሆናችሁ በመንግሥት ስልጣን ላይ ሆኖ ብልሹ አሰራርን የሚያራምዱትን አካላት ታግሎ በመጣልና አሰራሩን በማሻሻል ወደ ተሻለ ለውጥ ታመጡት ዘንድ ይቻላችኋልና በጉዳዩ ላይ ልትታትሩ ይገባልም ሲሉ አሳስበዋል።
«እኛ በጉባኤያችን 4 መሰረታዊ ችግሮችን ለይተን አይተናል። በእናንተም ውስጥ ይህ 4ቱ ነገር ተነስቶ በጥልቀት መታየት አለበት። ዴሞክራሲ ማለት በሰውነት ውስጥ ያለ የደም ዝውውር ማለት ሲሆን፤ ዝውውሩ ከተቋረጠ ሞት ያስከትላል። ስለዚህ የውስጥ ዴሞክራሲያችንም እንደ ደም ዝውውራችን መስራት ካልቻለ ድርጅታችን የሞት አደጋ ማጋጠሙ አያጠራጥርም። እናም ይህንን የውስጥ ዴሞክራሲን ማጠናከር ላይ ይህ ተረካቢ ትውልድ በስፋት ሊሰራ ይገባዋል። ከኢህአዴግ የበላይ አመራር ጀምሮ እስከታችኛው ታጋይ ድረስ መሰራትም ይኖርበታልም።» በማለት ድርጅቱ ያተኮረባቸውን ጉዳዮች አመላክተዋል።
መርህ አልባ ግንኙነትም እንዲሁ ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ ካሉት መካከል አንዱ ሲሆን የእናንተን ውህደት እንዳያጠፋና ነጻ የሀሳብ መንሸራሸር እንዳይኖር ያግደዋልና መጠንቀቅ ይገባችኋል። በአንድ ሀሳብና ግብ መጓዝ እንዳይቻል እድል ስለሚያመቻች በዲስፕሊን የተመራ፣ ድርጅታዊ ዲስፕሊን ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰብ፣ የአመለካከት አንድነት የመፍጠር ከዚያም አልፎ ይህንን አስተሳሰብ በማጎልበት ወደ ተግባር አንድነት የመለወጡ ኃላፊነት የዚህ ትውልድ ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ የህዝቦችን አንድነት ለማጎልበት፣ ከብሔራዊ ማንነት ባሻገር ኢትዮጵያዊ ማንነትን ያገዘ በመሆኑ የኢትዮጵያዊ ማንነት ጠንካራ አመለካከትን በተመለከተ በውስጣችን ምን አይነት አመለካከቶችን እያራመድን ነው የሚለውንም በትኩረት መዳሰስ ይኖርባችኋል። ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በጉባኤው አምስት ነገሮች ላይ አበክረው መወያየት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። ምክንያታቸው ደግሞ የውይይት ጉዳዮቹ ለኢህአዴግ ወሳኝ ችግር መፍቻ ቁልፎች መሆናቸው ነው።
የመጀመሪያው ለአገሪቱ የኢኮኖሚ ዋልታ ሆኖ እያገለገለ የሚገኘው ግብርና ሲሆን፤ ወጣቱና ዘመናዊ ግብርና ምን መምሰል አለበት በሚል ጉዳይ ላይ በስፋት ልትወያዩ ያስፈልጋል። ሁለተኛ ደግሞ የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ትራንስፎርሜሽን ማረጋገጥ ከወጣቶች አኳያ ምን መሆን አለበት በሚለው ላይ መወያየት ሲሆን፤ ምክንያቱ ደግሞ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ላይ በብዛት ተሳታፊው ወጣቱ ስለሆነ ነው። ሦስተኛው ወጣቱና ቴክኖሎጂ በምን መልኩ እየተጓዙ ይገኛሉ? በሚለው ላይ እንድትወያዩ ይፈልጋል። በአደጉት አገራት በርካታ ወጣቶች ቴክኖሎጂን በመጠቀም ህይወታቸውን ከመለወጣቸው ባሻገር አገር ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ እየሆኑ ነው። ስለዚህም እናንተም በዚህ ዙሪያ በስፋት ልትወያዩና የቀጣይ አቅጣጫ ልታስቀምጡ ይገባል።
አራተኛው ደግሞ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊነት ላይ መወያየት ነው። ልማታዊ ዴሞክራሲያዊነትን በምን ደረጃ እያስኬድነው እንገኛለን የሚለውን መፈተሽና ማየት አለባችሁ። በተለይ ተራማጅ ወጣቶች በዚህ ጉዳይ ላይ ያለን አተያይ ምንድነው? የሚለውን በሚገባ መፈተሽ ይጠበቅባችኋል። የዋና ከተማዋ ወጣቶች በመሆናችሁ ደግሞ ለአገሪቱ ምሳሌና መሪ ትሆናላችሁ ተብሎ ስለሚታመን ብሔርተኝነትና አክራሪነት ላይ ትኩረት አድርጋችሁ ልትወያዩ ያስፈልጋል። በመጨረሻ አደረጃጀታችሁ አዋጭ አደረጃጀት መሆኑን ለኢህአዴግ ማስመስከር ላይ መስራትና መወያየት አለባችሁም በማለት አምስት መሰረታዊ አቅጣጫዎችን ሰጥተዋል።
የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ተወልደ ገብረጻዲቅ በበኩላቸው፤ ኢህአዴግ አገሪቱን የሁሉም ህዝቦች እኩልነት የተከበረባት፣ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባትን መርህ ተከትላ እንድትንቀሳቀስ አድርጓታል። በተጨባጭም ከመበታተን ታድጓታል፤ አዲስ ዓይነት ዴሞክራሲያዊ አንድነትና የእኩልነት ትስስር በመገንባት ረጅም ርቀት እንድትጓዝ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላታል ካሉ በኋላ ዛሬም ይህንን ሁኔታ አስቀጥሎ እንዲጓዝ የሁሉም ማህበረሰብ እገዛ እንደሚያስፈልገው ያስረዳሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ የኢህአዴግ ታሪክ የሚጀምረው የወጣቱን ተሳትፎ ከማረጋገጥ ነው። በወጣት የተመራ ትግል በማድረግም ይታወቃል። ስለዚህ ከጥንት ጀምሮ ኢህአዴግ ወጣትነትን በሚገባ እየለካና ምን እንደሚያስፈልገው እያወቀ ተጉዟል። ዛሬም ይህንን ሀላፊነት ሲሰጠው ምን መስራት እንደሚችል ስለሚገነዘብ ነውና ወጣቱም የተሰጠውን ኃላፊነት በሚገባ መወጣት አለበት። ወጣቱ ትውልድ ይህንን አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ባህሬውን አስጠብቆ ለማስቀጠል በጉዳዩ ዙሪያ መምከር፤ ማስተማር፣ በየደረጃው ወርደው የተሰጡ ተግባራትንም በየጊዜው በጥልቀት በማየት ለመታደስ ራስን ዝግጁ ማድረግ ይኖርበታል።
መንግሥት እንደ መንግሥት የሰጠው ልዩ ትኩረት አለ፤ ድርጅቱ ደግሞ በዚያው ልክ ችግሮችን ለይቶ አስቀምጧል። በመሆኑም ወጣቱም ይህንን ተግባር በተለየ ሁኔታ አይቶ ሊተገብረው ያስፈልጋልና በተለያዩ መድረኮች እድሎች ሲመቻቹ ሁኔታውን በሚገባ ተገንዝቦ ወደ ተግባር መለወጥ ላይ መታተር እንዳለበት የሚገልጹት አቶ ተወልደ፤ በሕብረተሰባችን ዘንድ ህገመንግሥታዊ ሥርዓቱን፣ ልማታዊ አስተሳሰብና፣ በብዝሃነት ላይ የተመሠረተ ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማጠናከር ረገድ የተሰራው ሥራ አመርቂ ነው። ነገር ግን አሁንም መሰራት ያለባቸው ወጣት ተኮር ሥራዎች በርካታ ናቸው። ስለዚህም ወጣቱም ይህንን ሥራውን በቋሚነት ማስቀጠል ላይ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል ይላሉ።
የአዲስ አበባ ወጣቶች ሊግ ሊቀመንበር ወጣት ጥበቡ በቀለ በበኩሉ፤ ድርጅቱ በሊግ ከተመሰረተበት 1997 ዓ.ም ጀመሮ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። ሆኖም እንደ ኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ የተነሱት ክፍተቶች የጋራ ናቸውና በዚህ ሊግ ውስጥም ይታያሉ። በያገባኛል መንፈስ ችግሮቹን በጥልቀት የማየቱ ጉዳይም ትኩረት እንደሚኖረው ይናገራል። በተለይ ወጣት ተኮር ጉዳዮች ላይ በዋነኝነት የሚመለከተው ሊጉን ነውና እስካሁን ባሉት ተግባራት ውስጥ እያካተተ ሲሰራ ቢቆይም ክፍተቱ ግን ዛሬም አልተደፈነምና መስራት እንደሚጠበቅበት ያምናል።
የጉባኤው ዋነኛ ዓላማ ጥንካሬ ማጎልበቻ፣ ችግሮችን መለያና ከአገራዊ ብሎም ከከተማዊ እናት ድርጅቶች ወቅታዊና ተጨባጭ መረጃዎችን በመቀበል ወደ ተግባር መለወጫ መሆኑ ግልጽ እንደሆነ የሚናገረው ወጣት ጥበቡ፤ በጉባኤያቸው በተለይ ኢህአዴግ ችግሮቼ ናቸው ብሎ ከለያቸው ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩና የመፍትሄ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጡ አውስቷል። በጥልቅ የመታደሱ ሁኔታ በየደረጃው ሲከናወን ቢቆይም ዳግመኛ መታደስና ችግርን ማየት ደግሞ የበለጠ ለመሻሻል ምቹ ሁኔታን ይፈጥራልና አጋጠሙ በተባሉት የአመለካከትና የተግባር ችግሮች ከሊጉ ስትራቴጂካዊ ተልዕኮዎች አንጻር በመመርመርና ቆርሶ በመውሰድ ችግሮችን ከነምርጫቸው በማየት የሚሰራ ይሆናል ብሏል።
ዘመቻው ደግሞ የአንድ ወቅት ሳይሆን በየጊዜው ለውጦች የሚታዩበትና ውጤታማ መሆናችንን የምናስመሰክርበትም እንዲሆን ይሰራል፤ የሊጉ ተልዕኮ የህብረተሰቡን ለውጥ ማፋጠን፣ የሊጉን አባላት የትግል መድረክ ሆኖ ማገልገል፣ ለወከልነው ማህበረሰብ ጥቅም መረጋገጥ መታገል፣ የየወቅቱን የትግል መድረክ ተልዕኮ በቅጡ ማስፈጸምና ሁሉም ወጣት ተሳታፊ እንዲሆን ማረባረብ ነውናም በዚህ ላይ ጥልቅ የመታደስ ትግል ይደረጋልም ይላል።
እንደ ወጣት ጥበቡ ገለጻ፤ ኢህአዴግ እንደለያቸው ችግሮች ሁሉ ወጣት ሊጉም በራሱ የለያቸው ችግሮች አሉት። ለአብነትም የወቅቱን የትግል መድረክ የሚመጥን የአብዮተኛ ስብዕናን የተላበሰ ወጣት አለመኖሩ፣ የሊጉን ተልዕኮ በአግባቡ ማሳካት የሚችል ወጣት የልማት ሰራዊት ቁመና ያለመኖር፣ በሚፈለገው ደረጃ የወጣቱን መሰረታዊ ጥቅም ለማስከበርና ለማረጋገጥ የዝግጁነት ጉድለት መኖርና የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ባህሪን ይዞና ጠብቆ የመዝለቅ ችግሮች መኖራቸው በዋናነት ይጠቀሳሉ። ስለዚህም እነዚህ ችግሮች ላይ በስፋት በመወያየት ችግሩን በየደረጃ ለመፍታት የሚታተር ይሆናል።
ይህ የኢህአዴግ ወጣት ሊግ እንደ ሌሎቹ ክልሎች የህውሀት፣ የብአዴን፣ የኦህኦዴድና የደህዴን ተብሎ አልተዋቀረም። ምክንያቱም የከተማዋ ሁኔታ የህብሮች መኖሪያ በመሆኑ ይህንን ውህደት በጠበቀ መልኩ በኢህአዴግ ስድስተኛና ሰባተኛ ድርጅታዊ ውሳኔ መሰረት ህብረ ብሄራዊ የሆነ አደረጃጀት እንዲኖረው ተደርጎ የተመሰረተ እንደሆነ የሚገልጸው ወጣት ጥበቡ፤ ይህ መሆኑ ደግሞ ወጣቱ ብዝሀነቱንም ሆነ ህብረ ብሄራዊነቱን ጠብቆ እንዲጓዝ አድርጎታል። በተመሳሳይ በሰላሙ፣ በመልካም አስተዳደራዊ ግንባታ ሂደቱ በአንድነት እንዲጓዝና እንዲረባረብም ረድቶታል። በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሚፈጠሩት ችግሮች ዙሪያም በቅርብ በመነጋገር ችግሮቹ በምን ሁኔታ እንደተፈጠሩ በመረዳት ምን አይነት መፍትሄ መቀመጥ እንዳለበት አቅጣጫ ጠቋሚ መስመሮችን አስቀምጦበት ወጣቱን እየታደገበት መቆየቱን ይናገራል።
የጠባብነትና ትምክህትነት አስተሳሰቦችም በከተማዋ እንዳይንሰራፋና በተለይ ወጣቱን ያሳተፈ ችግር እንዳይፈጠር በማድረጉም ዙሪያ ሁነኛ አስተዋጽዖን እያደረገላቸው መሆኑንም ያስረዳል። በተለይም ሊጉ እንደ ኢህአዴግ የተደራጀ በመሆኑ ከአመራር ምርጫ ጀምሮ ችግር ያለበት ስላልሆነ በብሔራዊ መልክ እንዲታገሉ እንዲዳረጋቸው ይገልጻል። በእርግጥ ወጣቱ ከቴክኖሎጂ ጋር ባለው ቅርበት ከባድ ፈተናዎች ይገጥማሉ። በዚህም በሊጉ ውስጥ የአመለካከት ልዩነትና ሳያገናዝቡ የጸረ ዴሞክራሲ ትግል ውስጥ የሚገቡ ወጣቶች እንዲበራከቱ አድርጓል። ነገር ግን ጉዳዩ ይበልጥ እንዳይሰፋ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል፤ የመማማሪያ መድረኮችም ይፈጠራሉ። አስተምሮ ለመመለስም ትግል እየተደረገ መሆኑን ያስረዳል። በቀጣይም ጠንከር ያለ የፖለቲካ ሥራ በመስራት ህብረ ብሔራዊነታችንን አስጠብቆ ለመጓዝ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሷል።
ማንኛውም ማህበረሰብ ማሰብ የሚጠበቅበት ልማት ካለ፣ መልካም አስተዳደር ከሰፈነና አገሪቱ ካደገች ማህበረሰቡ ተሳትፎበት ነው። በዚያው ልክ ችግር ኖሮ ስህተቱ የተፈጸመ ከሆነም ከማህበረሰቡ የወጣ አካል ይህንን ብልሹ አሰራር መፈጸሙን ማመን ይገባል የሚለው ወጣት ጥበቡ፤ ወጣቱ ትውልድ በማስተማር ይህንን ችግር መፍታት ላይ መስራት ይኖርበታል፤ ሊጉም የተቋቋመው ለዚሁ ስለሆነ ትኩረት መስጠት አለበት ይላል።
በወቅቱ የፕሮግራሙ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል ከቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት የመጣችው ወጣት በላይነሽ ግርማ በበኩሏ፤ ወጣቶች ብዙ ኃላፊነቶች አለባቸው። አገር መምራት ይችላሉ፤ በዚያው ልክ ደግሞ አገርንም ማጥፋት ይችሉበታል። ስለሆነም የሚሳተፉበትን ነገር መለየት ይጠበቅባቸዋል። በተለይም የኢህአዴግ አባላት በዚህ ላይ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። ምክንያቱም አገርን ከሚመራው ድርጅት ጎን ለጎን የሚሰሩት በመሆናቸው ነው። እናም እንደተባለው ኢህአዴግ ችግሮችን ለይቶ ለማህበረሰቡ ይፋ እንዳደረገ ሁሉ እኛም የድርጅቱ አባላት ችግራችን ይህ ስለሆነ በራሳችን እንዴት እንፍታው? ብለን ልናስብና የመፍትሄ አቅጣጫ ልናስቀምጥ ይገባል።
« እያንዳንዱን ወጣት ከጥፋት ኃይል ልንከላከልለት ይገባል፤ መስመሩንም ማሳየት ከእኛ የኢህአዴግ ሊግ አባላት ይጠበቃል» የምትለው ወጣት በላይነሽ፤ ኢህአዴግ ችግሮቼ ናቸው ሲል ካስቀመጣቸው በተጨማሪ በሊጉ የተለዩ ችግሮችም አሉና እነርሱንም በማካተት በትኩረት ተመልክተን በሀቀኝነት በመተግበር መለወጥ ላይ በስፋት ሊሠራ እንደሚገባ አሳስባለች ።

 

ጽጌረዳ ጫንያለው

Published in ፖለቲካ

አብዛኛው የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ገቢ የሚገኘው ከወጪ ንግድ ነው። እንደ ንግድ ሚኒስቴር መረጃ ከሆነ በ2010በጀት ዓመት ስድስት ወራት ሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ የተገኘው ግን አንድ ነጥብ ሦስት አምስት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብቻ ነው። ገቢውም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው ጋር የ114 ነጥብ28 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብልጫ ቢኖረውም ከእቅዱ ጋር ሲነፃፀር የተገኘው 61 በመቶ ያህሉን ብቻ ሆኗል። በአገሪቷ የስድስት ወራት የወጪ ንግድ አስመልክቶ ሰሞኑን የንግድ ሚኒስቴር ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድሙ ፍላቴ በሰጡት መግለጫ እና ጥያቄዎች ላይ የተነሱ ጉዳዮችንም ይዘንላችሁ ቀርበናል።
ዝቅተኛዎቹ የወጪ ንግዶች
ከተያዘላቸው ዕቅድ አንጻር በገቢያቸው ከ50 በመቶ በታች ያስመዘገቡ የወጪ ንግድ ምርቶች መካከል ማዕድናት፣ የቁም እንስሳት ንግድ፣ የቆዳ አልባሳትና ዕቃዎች፣ የወተትና የሥጋ ምርቶች ይገኙበታል። በተጨማሪ የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓት፣ የተዘጋጀ ቅመም፣ መጠጥ፣ ሰም፣ የቅባት እህል ውጤቶች፣ ዓሳ፣ ወርቅ እና ብረታ ብረት አነስተኛ አፈጻጸም ታይቶባቸዋል። በተለይ የማዕድን ዘርፉ ከታቀደለት 323 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የተገኘው ገቢ 58 ሚሊዮን ያህሉን ብቻ ነው። ገቢው ሲታይም ዘርፉ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያሳያል።
ኢትዮጵያ በአግባቡ ልትጠቀም ካልቻለችባቸው ገቢዎች አንዱ የወርቅ ንግድ ሆኗል። በግማሽ ዓመቱ ሰባት ነጥብ 62 ቶን ወርቅ በመላክ 301ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ቢታቀድለትም የተገኘው ግን 47 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው። ይህም ከእቅዱ አንድ ስድስተኛ በታች አፈጻጸም ያሳያል። ዘርፉ አሳሳቢ የገቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በመታወቁም የኮንትሮባንድ ንግድን በመከላከሉ ረገድ የክትትልና የድጋፍ ሥራውን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ይታመናል።
ሌላው ዝቅተኛ አፈጻጸም የታየበት ዘርፍ የቁም እንስሳት ንግድ ነው። የበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የቁም እንስሳት ወጪ ንግድ ዕቅዱ በቁጥር 564 ሺ 852 እንዲሁም በገቢ ደግሞ 192 ሚሊዮን የሚጠጋ የአሜሪካን ዶላር ነው። ከዘርፉ የተገኘው ገቢ ግን38 ሚሊዮን ዶላር በመሆኑ የእቅዱን አንድ አምስተኛ ብቻ መሰብሰቡ መገንዘብ ይቻላል። የቁም እንስሳት አቅርቦቱ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በቁጥር ከፍተኛ ብልጫ ቢያሳይም በገቢ ደረጃ ግን ቅናሽ አሳይቷል። ለችግሩ እንደ ዋና ምክንያት የሚጠቀሰው ደግሞ የኮንትሮባንድ ንግድ መበራከቱ ነው።
ከተያዘላቸው ዕቅድ ከ50 በመቶ እስከ 74በመቶ ክንውን ያስመዘገቡ ምርቶች መካከል ኤሌክትሪክ፣ የተፈጥሮ ሙጫና ዕጣን፣ ቅመማ ቅመም፣ የብዕርና አገዳ እህሎች ፣የተዘጋጁ የፍራፍሬ ውጤቶች፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ አበባ፣ ዱቄትና ምግቦች፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ሥጋ፣ ታንታለም፣ የእንስሳት መድኃኒት፣ የጥራጥሬ ሰብሎች እና ጫማ ምርት ናቸው።
የተሻሉ የወጪ ንግዶች
ከተያዘለት ዕቅድ በላይ አፈጻጸም የተመዘገበበት የወጪ ንግድ ምርት የቅባት እህል ብቻ ነው። ቡናን በተመለከተ ከእቅድ በላይ ምርት ለውጭ ገበያ ቢቀርብም በገቢ ግን በዓለም ገበያ መቀዛቀዝ ጋር ተያይዞ ተገቢውን ምንዛሪ ማግኘት አልተቻለም።
የቅባት እህሎች በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ወጪ ንግድ 215 ሚሊዮን በላይ ገቢ በመገኘቱ አመርቂ ውጤት ታይቷል። ገቢውም ከእቅዱ 117 በመቶ በላይ በመሆኑ ለሌሎች ዘርፎች እንደ ምሳሌነት የሚቀርብ ሆኗል። አፈፃጸሙ ጭማሪ ያሳየበት ምክንያት ዘንድሮ የሰሊጥ ምርት በብዛት ተመርቶ ለገበያ በመቅረቡና የዓለም የገበያ ዋጋም በመጨመሩ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ላኪዎች ምርት በብዛት ገዝተው ኮንትራት በመግባት በወቅቱ ወደ ውጭ እንዲልኩ የተደረገው ክትትልና ድጋፍ ውጤት አስገኝቷል። በመሆኑም በቀጣይ ስድስት ወራት የተጀመረው ውጤታማ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል።
በሌላ በኩል የቡና ዘርፍ ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት ለዓለም ገበያ ማቅረብ ተችሏል። ባሳለፍነው ዓመት መጨረሻ ወደ ተግባር የገባው የቡና ሪፎርም በግብይቱ ላይ መነቃቃት ፈጥሯል። ከግብይት ተዋንያን እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ጠንካራ ቅንጅት በመፈጠሩም ከፍተኛ የቡና ምርት እንዲሰበሰብ በር ከፍቷል። 107 ቶን በላይ ቡና ለዓለም በማቅረብ 381 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ተሰብስቧል። ምርት ጨምሮ በገቢ ረገድ የ54 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ የደረሰበት ምክንያት ደግሞ የዓለም ገበያ ዋጋ መዋዠቅ ያመጣው ክስተት ነው።
በሌላ በኩል መካከለኛ አፈጻጸም ያሳየው ዘርፍ የቅመማ ቅመም ምርት ንግድ ሆኗል። የበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የቅመማ ቅመም ወጪ ንግድ ዕቅድ በመጠን 5ሺ 607ቶን እንዲሁም በገቢ ረገድ 10 ሚሊዮን ዶላር ነበር። ሽያጩም በመጠን 5ሺ ቶን በመሆኑ ገቢው የእቅዱን 66 በመቶ ሊደርስ ችሏል። በመሆኑም ያልተገኘውን ገቢ ለማካካስ በቀጣይ ወራት የተሻለ ምርት አቅርቦት እና ገቢ መሰብሰብ ይገባል። ዕቅዳቸውን ከ74 በመቶ እስከ 99በመቶ ክንውን ያስመዘገቡ ምርቶች ደግሞ እንደቅደም ተከተላቸው ሻይ ቅጠል፣ ቡና፣ ያለቀለት ቆዳ እና ጫት ናቸው።
ለገቢ መቀነሱ ምክንያቶች
የኢትዮጵያ ወጪ ንግድ በስድስት ወራቱ አፈጻጸም የ854 ነጥብ 76 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ጉድለት በማሳየቱ በቀጣይ ስድስት ወራት ጉድለቱን ለመሸፈን የሚያስችል የማካካሻ ሥራ ለማከናወን ያስፈልጋል። የግብርና ምርቶችን በተመለከተ በበጀት ዓመቱ የተመረተውን ምርት በወቅቱ ተሰብስቦ ወደ ገበያ እንዲወጣና የዘመኑ ምርት በተሻለ ጥራትና መጠን ለገበያ እንዲቀርብ ከክልሎችና ከግብይት ተዋንያን ጋር የተጀመረው ጥረት መጠናከር ይኖርበታል።
የቁም እንስሳትን በተመለከተ የግብይት ሥርዓቱ በሚፈለገው መልኩ ተግባራዊ አለመደረጉ እክል ሲፈጥር ቆይቷል። የህገወጥ የቁም እንስሳት ንግድን የመከላከል ሂደት ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለው ድጋፍ እና የክትትል ሥራ የተጠናከረ ባለመሆኑ በህገወጥ መንገድ የሚወጣው የቁም እንስሳት ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። በመሆኑም የህገወጥ ኮንትሮባንድ ንግድን መግታትና የዳልጋ ከብቶችን እንዲሁም የግመል ወጪ ንግድን በማሻሻል መስራት ያስፈልጋል። በተጨማሪም በዘርፉ የተለመዱ የገበያ የመዳረሻዎች ውስንነት ስላላቸው በህጋዊ መንገድም የመዳረሻ አገራትን ማስፋት ያስፈልጋል። እንደ አፍሪካ እና ዓረብ አገራት ያለውን ሰፊ የቁም እንስሳት ገበያ ለመጠቀም የሚያስችል የንግድ እንቅስቃሴ በሰፊው ማከናወን ይገባል።
የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች አፈፃፀምን ለማሻሻል ደግሞ በዋናነት ዝቅተኛ ደረጃ አፈጻጸም ያስመዘገ ቡትን ድርጅቶች በመለየት የሚስተዋ ሉባቸውን ችግሮች ለማሻሻል ጥረት ማድረግ አለባቸው። በአሁኑ ወቅት የዓለም ገበያ የሚጠይቀውን የተወዳዳሪነት መስፈርት ከማሟላት አኳያ በመስራት የተቀባይ አገራትን ይሁንታ ማግኘት ከአምራቾች ይጠበቃል።
የማዕድናት ምርቶች አፈፃፀምን በተመለከተ ከቁም እንስሳት ንግድ ጋር በተመሳሰለ ሁኔታ የወርቅ ንግድ ላይ ህገወጥ ግብይት ችግር እየፈጠረ ይገኛል። በህገወጥ መንገድ የሚባክነውን ምርት ለማስቀረት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ሥራዎችን በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል። በተለይ በኮንትሮባንድ ንግድ የወርቅ ሃብት ከአገር እየወጣ በመሆኑ የሚፈለገውን ገቢ ማግኘት አልተቻለም። በመሆኑም መንግሥት ያስቀመጠውን መመሪያ በመከተል ወርቅ እና የተለያዩ ማዕድናትን በህጋዊ መንገድ ለገበያ እንዲቀርቡ አምራቾችን መቆጣጠር ያስፈልጋል። በአጠቃላይ በተለይም በአሁኑ ወቅት ለኤክስፖርት አፈጻጸሙ ቁልፍ ችግር ከሆኑት መካከል አንዱ የኮንትሮባንድ ንግድ በመሆኑ ችግሩን ከህግ አካላት ጋር በመተባበር መከላከል ይገባል።
የገቢ ጉድለት በታየባቸው ምርቶች ላይ ትኩረት በመስጠት በቀጣይ ቀሪ ወራት በቅንጅት የተሻለ ሥራ በመስራት ምርቶቹ በስፋት እና በጥራት ለገበያ እንዲቀርቡ ማድረግ ያስፈልጋል። የአገሪቷ የወጪ ምርቶች በጥራት፣ በብዛት ለዓለም ገበያ በማቅረብ የገበያ ድርሻን ማስፋት አስፈላጊ ነው። ለሥራውም የውጭ ንግድ ዘርፍ የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንትን የማሳደግ፣ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ሁለገብ ድጋፍ መስጠት በተለይም የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የማስፋፋትና በሂደት ላይ ያሉ ኢንቨስትመንቶች ወደ ምርት ማሸጋገር ይጠይቃል።
ንግድ ሚኒስቴርም የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲገቡ ማበረታታትና መደገፍ እንዲሁም የገበያ መሠረት ልማትን የማጠናከር ሥራ እያከናወነ ይገኛል። የወጪ ንግድ እንዳይሻሻል እንቅፋት የሚሆኑ የሎጂስቲክስና የጉምሩክ አገልግሎት ችግሮችን በመቅረፍ በቀጣይ ስድስት ወራት የተሻለ ገቢ እንዲገኝ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። አምራች እና ነጋዴዎችም የገበያ አድማሳቸውን ለማሳደግ የሚያስችሉ የገበያ ማስተዋወቂያ ተግባራት ላይ በስፋት መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል።

 

ጌትነት ተስፋማርያም

Published in ኢኮኖሚ

በፈረንሳይ የወደብ ከተማ ካሌ በአፍጋናውያንና ኤርትራውያን በተነሳ ግጭት አምስት ስደተኞች ቆስለዋል። እድሜያቸው ከ16 እስከ 18 የሚሆኑ አራት ኤርትራውያንም አቅራቢያው ወደሚገኝ ሆስፒታል ተወስደው ቀዶ ህክምና የተደረገላቸው ሲሆን በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

አምስተኛው ሰው ጉዳቱ የከፋ በመሆኑ ወደ ተሻለ ህክምና ተወስዷል። በግጭቱ 13 ሰዎች በብረት ዱላ በመደብደባቸውም እንደቆሰሉ የአካባቢው ፖሊስ አስታውቋል። የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀራርድ ኮሎምብ አካባቢውን ከጎበኙ በኋላ ከሌላው በተለየ መልኩ አደገኛ ሁኔታ መኖሩን ገልፀዋል። አንደኛው በጣም የተጎዳው ሰው አንገቱ ጀርባ በጥይት እንደተመታም ተገልጿል። ለካሌ ነዋሪዎችም ሆነ ለስደተኞቹ መቋቋም የማይችሉዋቸው ግጭቶች እየበረቱ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
የመጀመሪያው ግጭት ለሁለት ሰዓታት ያህል የቆየ ሲሆን ስደተኞቹም ለምግብ ተሰልፈው በነበረበት ወቅት ነው ግጭቱ የተነሳው። በዚህ ግጭት ቁጥራቸው 100 የሚሆኑ ኤርትራውያንና 30 የአፍጋኒስታን ዜጎችም ተሳታፊ ነበሩ። ግጭቱም የተነሳው አንድ የአፍጋን ዜጋ ሽጉጥ በመተኮሱ መሆኑን የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ ያሳያል። በኤርትራውያን የተከበቡትን የአፍጋኒስታን ዜጎችን ለማዳን ፖሊስ አካባቢውን ከቦት እንደነበርም የአካባቢው አይን እማኝ ገልጿል።
ተጨማሪ የፈረንሳይ የፀጥታ ኃይል ወደ አካባቢው ተልኳል። የካሌ የስደተኞች መቆያ ወይም በቅፅል ስሙ ጫካው ተብሎ የሚታወቀው ቦታ ከሁለት ዓመት በፊት የፈረሰ ቢሆንም አሁንም ቢሆን ወደ እንግሊዝ ማቋረጥ በሚያስቡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች መኖሪያ ነው። በአካባቢው ያሉ የእርዳታ ድርጅቶች የካሌ ስደተኞችን 800ናቸው ቢሉም፤ ባለስልጣናቱ ከ550አስከ 600 እንደሚደርሱ ገልፀዋል።
የካሌ ጫካ ብሪታንያ ለመሻገር የሚፈልጉ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ስደተኞች ከውድቅዳቂ ላስቲክ፣ቆርቆሮ፣ ካርቶንና እንጨት በሰሯቸው ጎጆ እና ድንኳኖች ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ኖረው በታል። የፈረንሳይ ትልቁ የስደተኞች መሰብሰቢያ ሥፍራ ከመሆኑ በተጨማሪ የአሳዛኝ አኗኗር ምሳሌ በመሆኑም ዝናን ያተረፈ ቦታ ነበር። መጠለያው እንዲፈርስ ከመደረጉ በፊት እስከ 10 ሺ የሚደርሱ ስደተኞች ኖረውበታል። የያኔው የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ ያን የስደተኞች መከማቺያ ለማፈራረስ ፍላጎት እንዳላቸው በማስታወቃቸው ነበር እንዲፈርስ የተደረገው።
«ይሕን ጣቢያ ሙሉ በሙሉ እና በማያዳግም ሁኔታ ማፍረስ አለብን። ጨርሶ ማጥፋት አለብን። ሥደተኞቹን ሌላ ሥፍራ ሥናሰፍር ሰብዓዊነትንም ከግምት ማስገባት አለብን» በማለታቸው ትዕዛዛቸው ገቢር እንዲሆን ተደርጓል። በርካታ አውቶቢሶች ከተደረደሩ በኋላ በአንደ ጀምበር ብቻ ሰባት ሺህ ስደተኞች በመላው ፈረንሳይ በሚገኙ መጠለያዎች ተበተኑ። ከዚያም በያሉበት አካባቢ ሆነው የጥገኝነት ማመልከቻ እንዲያስገቡ ተጠየቁ። ለአካለ መጠን ላልደረሱ ጥቂት ስደተኞችን ግን ብሪታንያ ለመቀበል ፈቃደኛ ስለሆነች ፈረንሳይን ተሻግረው ሄዱ።
ምንጭ ፡-(አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እና ቢቢሲ)

አብርሃም ተወልደ

 

Published in ዓለም አቀፍ

በአሁኑ ወቅት የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን በኬንያ እያደረሰ ያለው የሽብር ጥቃት በአፍሪቃ ቀንድ ያለውን እንቅስቃሴ ያሳያል። «ታዋዊዛ» የተባለው የምስራቅ አፍሪቃ የጥናት ድርጅት እንዳመለከተው በኬንያና በሶማሌ የድንበር አቅራቢያ ቦታዎች ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ብቻ ከ50 በላይ የፖሊስ መኮንኖች በአልሸባብ መገደላቸውን አመልክቷል።
በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ የሚገኘው የዌስት ጌት የገበያ አዳራሽ ወከባ የበዛበት ነው። ቦታው ሸቀጦችን በቅናሽ ለመግዛት የሚፈልጉ ሸማቾች የቀንስ አትቀንስ ክርክር የሚያሳዩበት እና ህጻናት ልጆቻቸውን ለማስተኛት በመንሸራተቻ በሚገፉ ወላጆች የሚገኙበት አካባቢ ነው። በአዳራሹ ግድግዳ ጠርዝ ላይ የሚያስተጋባው የደህንነት ፍተሻ መሳሪያ ድምጽ ለአንዳንዶቹ ከፍተኛ የደህንነት ጥበቃን የሚያመለክት ሲሆን ለአብዛኛዎቹ የዌስት ጌት ሸማቾች ግን የተለየ ትርጉም አለው። ይህ ድምፅ በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር መስከረም 21 ቀን 2013 የ63 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈውን የሽብር ጥቃት የሚያስታውስ ነው።
ቀደም ሲል የተጠናከረ ፍተሻና ጥበቃ ያልነበራቸው የኬንያ የመገበያያ ቦታዎች አሁን አሁን በገበያ አዳራሾችም ይሁን በቤተክርስቲያናት እንዲሁም የማህበራዊ ጉዳይ በሚፈፀምባቸው ቦታዎች የታጠቁና በተጠንቀቅ የሚጠብቁ የፖሊስ መኮንኖችን ማየት የተለመደ ሆኗል።
በዌስትጌት የገበያ አዳራሽ የዶቼቬለው አንድሪው ዋሲከ ያነጋገራት ሽላ ንጉኒ የተባለች ሸማች የጥበቃው መጠናከር ደህንነት እንዲሰማት ማድረጉን ትናገራለች። ጆኒ ኪመኒ የተባሉ የዚሁ የገበያ አዳራሽ ደንበኛ በበኩላቸው ኬንያውያንን ከሽብር ጥቃት ለመጠበቅ የሀገሪቱ መንግሥት በርትቶ መስራት አለበት ይላሉ። በዌስትጌት የገበያ አዳራሽ ሲዘዋወሩ ስለ ሽብር ጥቃት የሚያስቡት አልፎ አልፎ ቢሆንም ቀደም ሲል በዚህ አዳራሽ በሽብር ጥቃት የተገደሉ ሰዎችን ግን መርሳት እንዳልቻሉ ይገልጻሉ።
ያም ሆኖ ግን የገበያ አዳራሹ እንደገና መከፈቱና ሥራ መጀመሩ ጥሩ ስሜት ፈጥሮ ላቸዋል። አሸባሪዎች የሽብር ጥቃት ሲፈፅሙና ህንፃዎችን ሲያወድሙ ዋናው ዓላማቸው ሰዎች በቦታው የመታሰቢያ መናፈሻዎችን እንዲገነቡ ነው። እኛ ግን በዌስትጌት ይህንን እንዲያደርጉ አልፈቀድንላቸውም ብለዋል።
ተዋዊዛ የተባለው ገለልተኛና ለትርፍ ያልተቋቋመ የምስራቅ አፍሪቃ የጥናት ድርጅት በቅርቡ የኬንያውያንን በደህንነት ስጋት፣ በፖሊስና በፅንፈኝነት ላይ ያላቸውን አስተያየት የሚያሳይ ጥናት አውጥቶ ነበር። በዚህ ዘገባው ታዲያ የሀገሪቱ ዜጎች በፍትህ ስርዓቱ ላይ ጥርጣሬ እንዳለቸውና በፖሊስ ላይ ያላቸው አመኔታም ቢሆን የተለያየ መሆኑን አመልክቷል።
አርባ ስምንት በመቶ የሚሆነው ኬንያዊ በፖሊሶች በህዝብ አገልግሎት ሥራ «ደስተኛ» ነን ሲሉ 33 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ አለመደሰታቸውን ይፋ አድርጓል። ድርጅቱ በ47 የኬንያ አስተዳደሮች አካሄድኩት ባለው ጥናትም በማህበረሰቡ ውስጥ ከሃምሳ ኬንያውያን ለአንዱ ሽብርተኝነት ቀዳሚ የደህንነት ስጋት ተደርጎ ይታያል። ነገር ግን ድርጅቱ በቀጥታ ጥያቄ ካቀረበላቸው አስር ኬንያውያን ስምንቱ ወደ 78 በመቶ የሚጠጉት ማለት ነው፤ አልሸባብ ለሀገሪቱ ዋና የደህንነት ስጋት ነው ብለው ያስባሉ ብሏል። በዚህም የተነሳ በርካታ ኬንያውያን የሀገሪቱ ሰራዊት በሶማሊያ እንዲቆይ ድጋፋቸው እየጨመረ መሆኑ ታይቷል ሲል ጥናቱ አመልክቷል።
የድርጅቱ ከፍተኛ የፕሮግራም ኃላፊ ቪክቶር ራቲንግ ጥናቱ የደረሰባቸው ተጨማሪ ጉዳዮች መኖራቸውንም ያብራራሉ። በሀገሪቱ ውስጥ የሽብር ጥቃት ዋና ጉዳይ ከመሆኑ በፊት ሰዎች ያለምንም ስጋትና ተጨማሪ ጥንቃቄ ወደፈለጉበት ቦታና ወደ መገበያያ ቦታዎች ይሄዱ ነበር። አሁን ወደ ዌስትጌት ብትሄድ ግን የስጋት ደረጃው በጣም ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ሪፖርቱ በእርግጠኝነት የሚለው በጣም ትልቅ ቁጥር መጠን ያለውና ወደ 80 በመቶ የሚሆኑ ዜጎች እስካሁን የአልሸባብ የሽብር ጥቃት ሰለባ እንሆናለን በሚል ስጋት ውስጥ ይኖራሉ። ነገር ግን በተመሳሳይ ሁኔታ የሚታየው ዜጎች የአክራሪ ሀይሉን እንዲቀላቀሉ የሚያደርጋቸው ምክንያት ምንድነው? ተብሎ ቢጠየቅ ብለን በምንጠይቅበት ጊዜ አብዛኛው የሚናገረው ስለስራ አጥነት ነው።
በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ከአልሸባብ የሽብር ጥቃት በተጨማሪ የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች የሀገሬውን ሰውም ይሁን የውጭ ሀገር ጎብኝዎችን ስጋት ላይ ጥሏል። ስለ ደህንነት ሲወራ ምርጫን ተከትሎ በመንግሥትና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ተፈጥሮ የነበረው ውዝግብና ግጭትም ሌላው ለሀገሪቱ ዜጎች አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ እንደነበር ተገልጿል። በተለይ የተቃዋሚ ፓርቲዎች «ራይላ ኦዲንጋ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ለመሆን ከሦስት ቀናት በፊት ቃለ መሃላ መፈጸማቸው ከደህንነት አንጻር የህዝቡ ጭንቀት ከፍ እንዲል አድርጓል። እናም ሀላፊነት ያለው መንግሥት ለህዝብ የሚበጀውን ሊያደርግ ይገባል ሲሉ ቪክቶር ራቲንግ መክረዋል።
ምንጩ፡-ዶቼዋሌ

አብርሃም ተወልደ 

Published in ዓለም አቀፍ


የታኀሣሥ ወር 2010 ዓ.ም የመጀመሪያ አጋማሽን በሁኔታዎች ግምገማ ቀጣይ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች ላይ ሲመክር የከረመው የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ካስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ስምንት አንኳር ጉዳዮች አንዱ የሚዲያዎች (የህዝብ መገናኛ ብዙሃን) ሚና ጉዳይ ነው። የጉባዔው መግለጫ እንዳስታወቀው በልማትና በሀገራዊ አንድነት ዙሪያ መትጋት ሲኖርባቸው ህዝብን ከህዝብ ጋር በሚያራርቅ አፍራሽ ተግባር ውስጥ የተሰማሩ የግልና የመንግስት የሚዲያ ተቋማት አካሄዳቸውን የሚያስተካክሉበት ሁኔታ ለመፍጠር ይንቀሳቀሳል።
በተለይም በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ ከፖለቲካዊ፣ ከህጋዊ አሠራርና ከህገ መንግስታዊ ስርአት በራቀ መልኩ የሁከትና የግርግር መልዕክት በህዝብ ሚዲያ የሚሰበክበትን ዕድል ለመዝጋት የሚያስችሉ የተቀናጁ እርምጃዎችንም ይወስዳል። ይህ ከፍተኛና ወሳኝ ችግር ነው መፍትሄው ግን ቀላል ነው። ማንም ግለሰብም ሆነ የሚዲያ ተቋም ከሀገርና ከሰላም በላይ አይደለም። የሩዋንዳ እልቂት መጠኑ እንደዚያ የገዘፈው በሚዲያ በተሰራጨ የተዛባና አውዳሚ መልዕክት ነው። ከዚያ እልቂት እንማራለን በአገራችን እንዲደገም አንሻም። የመንግስትና የግል ሚዲያው ስርአት እንዲይዝ ማድረግ ያስፈልጋል።
የመንግስቱን ሚዲያ በአስተዳደራዊ ርምጃ ማስተካከል ይችላል፤ የግሉን ሚዲያ ከተቻለ አቅጣጫ ማስያዝ ካልቻለ ደግሞ ፈቃዱን (ላይሰንሱን) ማስመለስ ወይም መንጠቅ ነው። የሚዲያዎች መብትና የአሰራር ነፃነት እንዲከበር እታገላለሁ። ያለምንም ጣልቃ ገብነት መስራት የሚችሉበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸው እመኛለሁ። ነገር ግን የአገርን አንድነትና ሰላም በሚያናጋ እና ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ፣ ነገር የሚያበርድ ሳይሆን የሚቀሰቅስ፣ የሚያባብስ፣ ለልማትና ለአገራዊ አንድነት ቅድሚያ ትኩረት የማይሰጥ ሆኖ ሲገኝ ከእርሱ መብት ይልቅ በህዝብ ላይ የሚደርሰው ጉዳት ይበልጣልና መስተካከል ወይም መቆም አለበት።
ለህዝቦች የማወቅ መብት፣ የመናገርና ሀሳብን በነፃ የማስተላለፍ መብት በህገ መንግስቱ የተቀመጠ ስለሆነ ሊከበር ይገባዋል። በዚህም ምክንያት ህዝቡ ለግል ሚዲያዎችና ለማህበራዊ ድረ ገጾች ጆሮውን የሚሰጠው ለምንድን ነው? ብሎ መንግስት ራሱን መጠየቅ አለበት። ህዝቡ በሌለ ገንዘብ ፌስቡክና ቲዊተር ላይ ተጥዶ የሚውልበትን ምክንያት መንግስት መመርመር አለበት። መልሱ ግልጽና ግልጽ ነው። መንግስት ስለተፈጠሩ ክስተቶች ተገቢና ወቅታዊ መግለጫዎችን መስጠት ስላልቻለ ነው፣ መረጃ አፍኖ ይይዛል፣ የተሟላ መረጃ አያቀርብም፣ ያዘገያል፣ በቃላት ጋጋታ መሃል ከዋናው ቁም ነገር ያዘናጋል! በቁጥርና በምስል አስደግፎ አያቀርብም። ጥቂት ግጭቶች፣ ጥቂት ግለሰቦች፣ ጥቂት ጉዳዮች፣ ጥቂት ጥቂት ብቻ ጥቂት ማለት ስንት ነው? መንግስት የሚያውቀው ቁጥር «ጥቂት» ብቻ ነው ማለት ነው? አብራርቶ መናገር መቻል አለበት። ይህን ማድረግ ካልቻለ ግን የህዝቡን መረጃ ተደራሽነት መብት ለማረጋገጥ የሚሰሩትን የግልና ማህበራዊ ሚዲያዎችን ሊወቅስ አይችልም። በእርግጥ በአለም ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች እንዳሳዩት ከሆነ ማህበራዊ ሚዲያ የሚባሉት ድረ ገጾችን ተሰሚነታቸውና ተአማኒነታቸው ቀንሷል። እንኳን የሚያ ምናቸው ሥራ ፈትቶ የሚሰማቸው ሰው ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ ነው።
«ኤደል ማን ትረስት ባሮሜትር» የተባለ የእንግሊዝኛ የገበያና ጥናት ተቋም ይፋ ባደረገው ጥናት መሰረት ከብሪታንያውያን ተጠያቂዎች ማህበራዊ ሚዲያውን የሚያምኑት 1/4 ነው /ከአራት አንድ/ ሰው ብቻ ነው። ሶስቱ አያምኑም። እድሜያቸው ከ16 እስከ18 የሚሆኑ 3000 ሰዎች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ ማህበራዊ ሚዲያው ግልጽነት የለውም የሚሉት 63ከመቶ ያህል ናቸው። ህግና ደንብን በመከተል ረገድ 64በመቶ ተጠያቂዎች ማህበራዊ ሚዲያዎች ለህግ ተገዢ አይደሉም ባዮች ናቸው።
50 በመቶ ሰዎች ማህበራዊ ሚዲያ የሚያሰራጨው ሀሰተኛ ወሬ (Fake News) ነው ብለው ያምናሉ። 62በመቶ ያህሉ ተጠያቂዎች ማህበራዊ ሚዲያ የሌሎች ሰዎችን መረጃ (ዳታ) ያለባለቤቶቹ ፈቃድና እውቅና እያወጡ እንደሚሸጡ ያምናሉ። «የዘረፋ ቤት ነው» ባዮች ናቸው። 64 በመቶ ያህሉ በመደበኛው ጋዜጠኝነት (proper jour nalism)እና በፈጠራ ወሬ መካከል ያለውን ሁኔታ መለየት አልቻልንም ብለዋል። እንደ ፌስቡክና ትዊተር ያሉት አቀራረቦች (ፕላትፎርምስ) በገጾቻቸው የሚያሰራጩትን ህገወጥና ኢ-ስነምግባራዊ መልዕክት መቆጣጠር አልቻለም፤ የጥላቻ ንግግርንና ጽንፈኝነትን (አክራሪነትን) መስመር ማስያዝ አልቻሉም። በዚህ የተነሳ የህዝቡን አመኔታ /public trust/ እና ድጋፍ እያጡ ነው።
በአንፃሩ ደግሞ ባህላዊ (የተለመደው) ጋዜጠኝነት እንደ ብሮድካስትና ህትመት ያሉት ሚዲያዎች ተአማኒነት በ13በመቶ ጨምሮ አሁን 61በመቶ ላይ ደርሷል። ማህበራዊ ሚዲያ በአሁኑ ሰዓት በጣም አሰልቺ ቅጥፈት የበዛበት፣ ለአንድ ወገን የሚያደላ፣ ሚዛናዊነት የጐደለው፣ በድብቅ አጀንዳ የተሞላ ነው። ከማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ከፊል ያህሎቹ አርዕስቱን ብቻ አይተው (Skim) የሚያልፉ እንጂ ዝርዝሩን ለማየት ክሊክ የማያደርጉ ናቸው፤ሁለት ጐራዎች አለበት። ርዕስ ጉዳዩን (አርዕስቱን) ብቻ የሚመለከቱ (New Skimmers) እና ዜናውን ጨርሶ የማይፈልጉ (News avoiders) ማህበራዊ ሚዲያና በአለም ዙሪያ ተፈላጊነቱን፣ ተአማኒነቱን፣ ተደጋፊነቱን እያጣ ነው። ስለልማትና ስለሰላም፣ ስለ አገራዊ አንድነትና ስለህዝቦች አብሮነት ማራመጃነት አልዋለም። ሥራው በሙሉ አንድነትን ማናጋት፣ ሰላምን መበከል፣ ህዝቦችን ማጋጨት ነው። ሲፈጠር አላማው ለዚህ አልነበረም። ለህዝቦች መልካም ግንኙነት መረጃን፣ ሃሳብን፣ ፈጠራንና የንግድ ሥራን ማሳለጥ ነበር።
ለአገር አንድነትና እድገት የሚያስፈልገን ልማታዊና ሰላማዊ ጋዜጠኝነት (PJ) ነው። የሰላም ጋዜጠኝነት የሚባለው በህዝቦች መካከል ሊነሱ የሚችሉ ግጭቶች፣ መሰረታዊ ምክንያቶችና ግጭት ሊጭሩ የሚችሉ ሰበቦችን በጥልቀት የሚመረምር ነው። የሁለቱም ወገኖች ችግሮች ለማዳመጥ እድል በመስጠት ግጭቶች ከመፈጠራቸው በፊት የጋራ ውይይት የሚደረግበትን አቅጣጫ ያሳያል። ትክክለኛ የመፍትሄ ሃሳቦችን ያፈልቃል። ሁሉም ወገኖች ወደ ሰላም እንዲመጡ ለአካባቢያቸው ሰላም ለአገሪቱ አንድነት በጋራ እንዲሰሩ ያበረታታል።
የሌለ ግጭትን አይዘግብም፤ ጥቃቅን ግጭቶችንም አያራግብም፤ ህዝብ እርስበርስ እንዲጨራረስ አይሰራም፣ ህዝብን ከህዝብ አያራርቅም፤ በአፍራሽ ተግባራት ውስጥም አይሰማራም። የሁከትና የግርግር መልዕክት አያሰራጭም፣ መንግስትን መቃወም የሚቻልና የሚያስፈልግ ቢሆንም ይህን ለማድረግ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረግ ከህገ መንግስታዊ ስርዓት የራቀና ተቀባይነት የሌለው ነው። በዚህ መንፈስ ወደ መደበኛውና ትክክለኛው የልማትና የሰላም ጋዜጠኝነት ሥራችን እንመለስ ልማትን በተመለከተ ሚዲያው የሚሰራቸው በርካታ ሥራዎች አሉ። የአሁኑ ዘመን የሚዲያው የልማት የትኩረት አቅጣጫ ፀረ-ሙስና ትግሉን ማጠናከር ነው።
በያዝነው ዓመት በእኛ 2010 ዓ.ም በፈረንጆቹ 2018 በአፍሪካ መሪዎች ሥራ አስፈፃሚ ስብሰባ ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው ፀረ ልማት ተግባራት ዋናው ሙስና መሆኑ ተሰምሮበታል። አፍሪካ የገንዘብ (የፋይናንስ) አቅሟን ለማጐልበት አቅም ያጣችው በገንዘብ ማሸሽና በሙስና ምክንያት ነው። አፍሪካ በየዓመቱ 150 ቢሊዮን ዶላር ታጣለች። ለበርካታ አገራዊ ልማቶች፣ ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለኑሮ፣ ለመንገድ፣ ለሥራ አጥነት መቀነስ፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠሪያ የሚሆን ግዙፍ ገንዘብ በሙስና ምክንያት ይባክናል። ፀረ ሙስና ትግላችንን አጠናክረን መቀጠል ብንችል ያለምንም የውጭ እርዳታ ራሳችንን ነበር። በአሁኑ ወቅት ሙስና ከአሸባሪነት በላይ መሆኑ በአፍሪካ 30ኛ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የመከሩት ሥራ አስፈፃሚዎች አረጋግጠዋል።
አሸባሪነት በአህጉራቱ ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት ይልቅ በሙስና ገንዘብ ማሸሽ የበለጠ እስኪጐዳን ድረስ እጃችንን አጣጥፈን መቀመጥ የለብንም። ትርጉም ያለው ፀረ ሙስና የሚዲያ ሥራ መስራት አለብን። ለሙስና ትኩረት መስጠት አለብን። በየደረጃው ከሚደረጉ የኪራይ ሰብሳቢነት እንቅስቃሴዎች አንስቶ በከፍተኛ ደረጃ ከአገር እስከ ስለሚሸሹ ገንዘቦች ድረስ ከመነሻ እስከ መዳረሻቸው ያለውን ሂደት ተከታትለን ቆፍረን ለእርምት ማብቃት አለብን።
ሙስናና ብልሹ አሠራሮች እንዲወገዱና የመንግስት የፋይናንስ አጠቃቀም ግልጽነት ኖሮት ኃላፊነት ያለበትን አካል ተጠያቂ ለማድረግ እስኪቻል ድረስ ሚዲያው መስራት አለበት። በስደት ጉዳይ ዙሪያም ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል። በሊቢያ ስደተኞች ላይ የሚደርሰው የባሪያ ንግድ 100 ዓመት ወደኋላ የሚመልሰን ነው። እንደ አገር ኢትዮጵያ በሊቢያ የሚገኙ ስደተኞቿን ወደ አገራቸው በመመለስ በባለስልጣኖች በኩል አቀባበል አድርጋለች። በየአካባቢው የተፈጠረው ቀውስ ኢኮኖሚያዊ ይሁን ፖለቲካዊ መንስኤው የሰላም አለመኖር ነው። ባሪያ የሚሸጠው በሊቢያ ሰላም ስለሌለ ነው፤ ከየመን ሶሪያ፣ ኤርትራ የሚጐርፈው ስደተኛም በሰላም ችግር ምክንያት ነው።
ሰላም ከጠፋ ሥራ አጥነት ይስፋፋል። ለዚህ ሲባል ባህር አቋርጦ መሄድ ግድ ይሆናል። በዚህ መሃል የባህር እራት መሆን አለበት። ያንን ሁሉ የበረሃም መንገድ አቋርጦ፣ የተፈጥሮን ሰው ሰራሽ ችግሮች ችሎ ጀልባ የተሳፈረው ስደተኛም ወደአሰበው ቦታ በሰላም ለመድረሱ ዋስትና የለውም። «ካልደፈረሰ አይጠራም» የሚለው አባባል አይደለም፤ ሰላም ከደፈረሰ መቆሚያ የለውም። «ድፍርስ ይጠራል» ስንል «ድፍርሱ ይበልጥ ሲደፈርስ የተሻለ ይመጣል» ስንል የባሰ ሊመጣ ይችላል። ሰላማችንን አጥብቀን ከመያዝ ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም። ለራሳችንና ለልጆቻችን ስንል አገራዊ አንድነታችንን አጠናክረን እንቀጥል።
በመጨረሻም ባሳለፍነው ጥር ወር ከገና ጀምሮ ጥምቀትን ጨምሮ የነነዌ ጾምን ጀምሮ ብዙ ሃይማኖታዊ በአላትን አክብረናል። አሁን ደግሞ ለተዋህዶ ክርስትና ተከታዮች ዐቢይ ጾም ከዛሬ ሳምንት የካቲት 5/2010 ዓ.ም ጀምሮ ይገባል። ሁለት ወር የጾም የፀሎት ጊዜ ነው። የረብሻና የግጭት የጥላቻ ንግግር ጊዜ አይደለም። ይህን ከግምት አስገብተን ፈጣሪ ለአገራችን ሰላም እንዲያወርድልን፣ ህዝባችንን እንዲጠብቅልን፣ መንግስትንም ማስተዋልን ጥበብን እንዲሰጥልን የምንማፀንበት ጊዜ ነው። ሰላምና ለአገራዊ አንድነታችን እንፀልይ፤ ሚዲያውም ደግ ደጉን ያሰማን

ግርማ ለማ

Published in አጀንዳ

የንግዱንና የሸማቹን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግና ፍትሃዊ የንግድ ውድድር ለማስፈን፤ ፈጣን ልማትና የመልካም አስተዳደር ስርዓትን ለመገንባት የንግዱንና ሸማቹን ህብረተሰብ የሚያስተናግዱ ህጎች ተቀርጸው ተግባራዊ ተደርገዋል። ስራ ላይ በመዋላቸው ደግሞ የተሻለ የንግድ ስርዓት እንደተዘረጋ ይታመናል፡፡
ለዘመናት ስር ሰዶ በቆየው ኋላቀር እና የተዛባ አሰራር ኪራይ ሰብሳቢነት በሰፊው የተንሰራፋበት፣ ህገወጥ ንግድ ጎልቶ የሚታይበት፣የዘርፉን እድገት የሚመጥን አደረጃጀትና አሰራር ያልተተገበረበት ሆኖ ቆይታል። ይሁን እንጅ አገሪቱ በምትከተለው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መሠረት ተገቢውን አሠራር ተከትሎ የሚካሄድ የግብይት ስርዓት መሆን ነበረበት።
በተለይም የንግድና የግብይት አሰራሩን ከተዛባ ተገቢ ባልሆነ የንግድ ውድድር ሸማቾች በኢፍትሃዊ የንግድ አሰራር ተጠቂ መሆናቸው አይቀሬ ይሆናል። በተጨማሪም መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች የሚደበቁበት፤ ጥራታቸው የተጓደሉና ደረጃቸውን ላልጠበቁ ምርቶችና ለአገልግሎት የተጋነነ ዋጋ የሚጠየቅበት፤ ለጤና ጎጅ የሆኑ ምርቶች የሚቀርቡበት፤ዋጋ በስምምነት የሚወሰንበት፤በግብይት ሰንሰለት መራዘም ውስጥ የደላሎች ያልተገባ ጣልቃ ገብነትም ይፈጠራል። በእነዚህ ችግሮች የሚጎዳው ደግሞ ሸማቹ በመሆኑ የንግድ ስርዓቱ ማዘመን እንዲሁም በህግና ስርዓት መምራት ያስፈልጋል፡፡
ይህን ችግር አስቀድሞ የተረዳው መንግሥት እነዚህን መሰረታዊ የሆኑ ችግሮች ለማቃለል፤ የንግዱን ማህበረሰብ ከፀረ ውድድር እና ተገቢ ካልሆኑ የገበያ ተግባራት ለመታደግ፤ እንዲሁም ሽማቹን ማህበረሰብ መብት ለማስጠበቅና ነፃ ገበያ ውድድርን ለመፍጠር ተሻሽሎ የወጣውን የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813 ን በ2006 ተግባራዊ አድርጓል፡፡
የአዋጁ መውጣት ቀዳሚው ዓላማ የንግዱን ማህብረሰብ ከፀረ-ውድድርና ተገቢ ካልሆኑና ህገወጥ የገበያ ተግባራት፤ ሸማቹን ከሚያሳስቱ የገበያ ሁኔታዎች የሚከላከልና ለነፃ ገበያ ውድድር አመቺነት ያለው ድርጊት ለመፍጠር ነው፡፡በተጨማሪም ለሸማቹ ደህንነታቸውና ለጤንነት ተስማሚ የሆኑ ምርቶች እንዲቀርቡ፤ ላወጣባቸው ዋጋ ተመጣጣኝ የሆነ እቃዎችና አገልግሎቶች ማግኘት የሚችልበት ሁኔታ ለማመቻቸት ነው።
ይሁን እንጅ አሁንም አንዳንድ ነጋዴዎች ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌላቸው የዋጋ ጭማሪዎች አድርገው በገበያው ላይ ውዥንብር ሲፈጥሩ፣ ላልተገባ ወጭ ሲዳርጉና ኑሮ ላይ ጫና ሲፈጥሩ ይስተዋላሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም ለጤና ጎጅ የሆኑ ምርቶችን ወደ ገበያ በማስገባት የሸማቹን ጤንነት ለአደጋ በማጋለጥ ላይ ናቸው። በእነዚህ ላይ ተገቢውን እርምጃ መወሰድ አለበት፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት በተከናወነ ስራም ተገቢ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ፣ ሸማቹ ላይ የተለያዩ አሉታዊ ተፅዕኖችን የፈጠሩ 214 ንግድ ተቋማት ላይ ማጣራት ተደርጎ 62 የንግድ ድርጅቶች ላይ ክስ ተመስርቷል። በተጨማሪም 42 የንግድ ሱቆች እንዲታሸጉ ተደርጓል፤ የዋጋ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው አሉ። የ119ኙ ጉዳይ ደግሞ በክርክር ሂደት ላይ እንደሚገኝ ከንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን የተገኘ መረጃ ያሳያል።
መረጃው እንደሚያሳየው መንግሥት የ15 በመቶ የብር የመግዛት አቅምን መቀነሱን ተከተሎ ጥቂት የማይባሉ ነጋዴዎች የዋጋ ጨማሪ ሲያደርጉ ተይዘዋል። በእንስሳት መድሃኒት አቅርቦት ላይ ከ2 ነጥብ 8 በመቶ እስከ 140 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ነጋዴዎች ነበሩ። በብረት ንግድ ላይ ከተሰማሩ መካከል 50ዎቹ ላይ ምርመራ ተደርጎባቸው ችግር በተስተዋለባቸው 16 ድርጅቶች ላይ ክስ ተመስርቷል። በተለይ በብረት ንግድ ላይ ከ50 በመቶ በላይ ጭማሪ ያደረጉ ነጋዴዎች ምክንያታቸው አሳማኝ ባለመሆኑ ለህግ እንዲቀርቡ መደረጉ ለሌሎች ማስተማሪያ ስለሚሆን የፍርድ ሂደቱ ለህዝብ ይፋ ሊደረግ ይገባል። በተመሳሳይ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚደረገው ማጣራት እና የክስ ሂደት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
ለህብረሰተቡ የሚቀርቡት መሰረታዊ የምግብ ፍጆታዎች ላይ መንግሥት ከፍተኛ ድጎማ እንደሚያደርግ ይታወቃል። ይሁን እንጅ በአንዳንድ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት የሸማቹ መብት ሲጣስ ተስተውሏል። በመሆኑም ምርቶቹ ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ የመከታተልና የመቆጣጠር ሥራው ከመንግስት በተጨማሪ የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት መሆን ይገባዋል።
የግል ጥቅማቸውን ለማካበት የሚፈልጉ የሸማቾች ማህበራት ሰራተኞች በሚፈጽሙት ህገወጥ ተግባር ከሸቀጦቹ ህጋዊ የስርጭት መስመር ውጪ ለሚገኙ ነጋዴዎች ምርቶችን እንደሚያቀርቡ ተረጋግጧል። ችግሩም የምርት እጥረት እንዲፈጠር በማድረግ በሸማቾች ላይ ምሬት ፈጥሯል። በሌላ በኩል የፍጆታ እጥረት እንዲፈጠር ከነጋዴዎች ጋር ያለአግባብ የሚተሳሰሩ የሸማች ማህበራትን መኖራቸውም ተረጋግጧል።
በተለይም መንግሥት ድጎማ በሚያደርግባቸው ስኳር እና ዘይትን ለህገወጥ ነጋዴዎች በማቅረብ የሚሰሩ እና ተቀባይ ግለሰቦች ላይ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ማስተማርያ ማድረግ ይገባል። በህገወጥ መንገድ የሚከማች፣ ሲጓጓዝ እና ሲሸጥ በሚገኝበት ምርት ካለ ህብረተሰቡ በአካባቢው ለሚገኙ ንግድ ቢሮዎች እና ለህግ አካላት ጥቆማ በመስጠት ማጋለጥ ይኖርበታል። ችግሮች በተከሰተባቸው የህብረት ስራ ማህበራት ሱቆች እና ህገወጥ ነጋዴዎች ላይ ፈጣን እርምጃ በመውሰድ የሸማቹን እምባ ማበስ ይገባል።

Published in ርዕሰ አንቀፅ

ለወራት የሙከራ ስርጭት ላይ የነበረው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አካል የሆነው ፋና ቴሌቪዥን በፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ በይፋ ተመርቆ ስራ ጀመረ። ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ በምርቃቱ ወቅት በሀገራችን የቅርብ ጊዜ የመገናኛ ብዙሃን ታሪክ ውስጥ የነበሩ መልካም ተግባራት እንዳሉ ሆነው ከስነ-ምግባርና ሙያዊ መለኪያዎቸ አንጻር ግን በርካታ ችግሮችን አስተውለናል ብለዋል። ይሄውም ጥሩ መስሎ የሚታያቸውን ብቻ በማድነቅና በማጉላት የሚዘግቡ መገናኛ ብዙሃን በአንድ በኩል ስናይ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተሰራውንና ያለውን መልካም ነገር ለማየት ለመስማትና ብሎም ለመዘገብ ፍላጎት የሌላቸው መገናኛ ብዙሃንም እንዳሉ ከማንም የተሰወረ አይደለም። የማሞገሱም ሆነ የማንቋሸሹ ሁለቱም ጫፎች ጉዳት እንጂ ጥቅም አላተረፉልንምም። ጥርጣሬ እንጂ የህዝብ አመኔታን አላስገኙምበመሆኑም ከእነዚህ ሁኔታዎች ብዙ የምንማራቸው ነገሮች እንዳሉ መገንዘብ በአሁኑ ጊዜ ለሀገራችን የሚያስፈልጋት በሙገሳ ብቻ ሳይሆን ወይም በጥላቻ ላይ የተንጠለጠለ መገናኛ ብዙሃን ሳይሆን ሚዛናዊ በህዝብ ዘንድ አመኔታ ያተረፈ እና በአጠቃላይ ለሃገራችን ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ጥቅሞች የሚቆረቆር መሆን ይኖርበታል ሲሉ ተናግረዋል። እንዲህ ዓይነት መገናኛ ብዙሃን እንዲፈጠር ለማድረግ ደግሞ ኃላፊነቱ የመንግስት ብቻ ሳይሆን በዋናነት በሙያው ውስጥ ያሉ አመራሮች እና ጋዜጠኞች መሆናቸው ልብ ሊባል ይገባል በማለት ፐሬዝዳንቱ ገልጸዋል።  

ፋና ቴሌቪዥን የመጀመሪያ ዙር ወጪው 255 ሚሊዮን ብር እንደፈጀ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አሰፈጻሚ አቶ ወለዱ ይመሰል ተናግረዋል።። ድርጅቱ ፈታኝ ጊዜያትን እንዳሳለፈ ሁሉ ስኬታማ ጊዜያትን በማሳለፍ አትራፊ መሆኑን እና በአመት ከትርፍ ግብር 17 ሚሊዮን ብር ለመንግስት እየከፈለ መሆኑን በወቅቱ ተገልጿል።

በጌትነት ተስፋማርያም

Published in የሀገር ውስጥ

በሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሞሮኮ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የቆየው ውድድር (ቻን) ተጠናቆ፤ ቀጣይ አዘጋጅነቱን ለኢትዮጵያ ሊያስረክብ የአንድ ቀን ዕድሜ ብቻ ይቀረዋል። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በአህጉሪቷ ያለውን የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ለማጠናከር በማሰብ፤ በአገር ውስጥ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት ሻምፒዮና በየሁለት ዓመቱ ያካሂዳል። በዝግጅት ማነስ ከኬንያ የተቀማው 5ኛው የቻን ውድድርም 16 የአፍሪካ አገራት መካከል ሲያካሂድ ቆይቶ በነገው የፍጻሜ ጨዋታ መቋጫውን ያገኛል።
በቶታል ስፖንሰር አድራጊነት የሚካሄደውን ይህንኑ ውድድርም ሞሮኮ በአራቱ ዘመናዊ ስታዲየሞቿ አስተናግዳለች። በፈረንጆቹ የጥር ወር አጋማሽ ተጀምሮ በየካቲት ወር መጀመሪያ በሚጠናቀቀው ውድድርም በአገር ውስጥ ሊጎች ብቻ የሚጫወቱ ተሳታፊዎች ሲሆኑበት ቆይተዋል። በግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ተሸንፈው ለደረጃ የበቁት ሱዳንና ሊቢያ ዛሬ በማራካች ስታዲየም በሚካሄደው ጨዋታ የሚለዩ ይሆናል። በምድብ አንድ አዘጋጇ ሞሮኮም በምድብ ሦስት ከተደለደለችው ናይጄሪያ ጋር ነገ ለዋንጫው የሚፋለሙ ይሆናል።
የናይጄሪያ ተጫዋቾች (ንስሮቹ) በተደለደሉበት ምድብ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከሩዋንዳ ጋር ሲያደርጉ ያጠናቀቁት ምንም ዓይነት ነጥብ ሳያስመዘግቡ ነበር። በውድድሩ ከታዩ ጠንካራ ብሄራዊ ቡድኖች መካከል አንዷ የሆነችው ሊቢያ በቀጣይ ጨዋታ የተገናኙት ንስሮቹ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ነበር መርታት የቻሉት። በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታም ኢኳቶሪያል ጊኒን 3ለ1 በሆነ ሰፊ ግብ አሸናፊነታቸውን በማረጋገጥ ወደ ሩብ ፍጻሜ የሚያደርጉትን ጉዞ አፋጥነዋል።
በሩብ ፍጻሜው ከምድቧ ሁለተኛ ከሆነችው አንጎላ የተገናኘው የናይጄሪያ ብሄራዊ ቡድን 2 ለ1 በሆነ ውጤት ግማሽ ፍጻሜውን ሊቀላቀሉ ችለዋል። በዘንድሮው ውድድር ጠንካራ ሆኖ ከቀረበው የሱዳን ብሄራዊ ቡድን ጋር በተካሄደው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ላይም፤ ንስሮቹ በ16ኛው ደቂቃ ቀዳሚ በሆኑባት ብቸኛ ግብ ለፍጻሜው ጨዋታ መድረሳቸውን አረጋግጠዋል።
አዘጋጇ ሞሮኮ በምድቧ ሞሪታኒያ ላይ አራት ግቦችን በማስቆጠር የአሸናፊነት ጉዞዋን የጀመረች ሲሆን፤ ጊኒን 3ለ1 በሆነ ውጤትም አሸንፋለች። ከሱዳን ጋር በተደረገው የመጨረሻ የምድብ ጨዋታም ያለምንም ግብ በመለያየታቸው በግብ ተበላልጠው ከምድባቸው በእኩል ነጥብ ሊቀመጡ ችለዋል።
በሩብ ፍጻሜው ናሚቢያን ያስተናገዱት የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች (የአትላስ አምበሶች) ከእረፍት በፊትና ከእረፍት በኋላ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅለዋል። በግማሽ ፍጻሜውም እ.አ.አ የ2014 ሻምፒዮናዋ ሊቢያ ከእረፍት በኋላ በተቆጠሩባት ሁለት ግቦች እንዲሁም በጭማሪ ሰዓት በተገኘ የቅጣት ምት ሦስት ግቦች ተቆጥረውባት ልትሸነፍ ችላለች።
እ.አ.አ የ2012 እና 2015ቱን የአፍሪካ ዋንጫ ያነሱት ንስሮቹ፤ በዓለም እግር ኳስ ተቆጣጣሪው አካል ፊፋ በየወሩ በሚሰጠው የአገራት የእግር ኳስ ደረጃ መሰረት 51ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ብሔራዊ ቡድኑ በ2014ቱ ቻን ዋንጫውን ለማንሳት የነበረው ግስጋሴ በጋና ብሄራዊ ቡድን ቢስተጓጎልም ዚምቧቡዌን በመርታት ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠበት በመድረኩ ያስመዘገበው ከፍተኛ ውጤት ነው። የብሔራዊ ቡድኑ አባላት በዚህ ሻምፒዮና የሚያሳዩት ብቃት ወደ ሩሲያ በሚያቀናው የዓለም ዋንጫ ቡድን ለመካተት ዕድሉን ስለሚያመቻችላቸው ለአሸናፊነቱ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ነው የሚጠበቀው።
የአትላስ አንበሶች ያለፈው ወር በእግር ኳስ ደረጃቸው ከዓለም 39ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ይሁን እንጂ ሞሮኮ በቻን ተሳትፎዋ ያላት ከሩብ ፍጻሜ ያልዘለለ ውጤት ነው። ራሷ ባስተናገደችበት በዚህ ውድድር ላይ ቡድኗን አጠናክራ የቀረበች ሲሆን፤ የቡድኑ አባላትም ከታዋቂዎቹ የካዛብላንካ የደርቢ ቡድኖች ዋይዳድና ራጃ የተውጣጡ ናቸው ተብሏል።
በቀጣዩ የሩሲያ ዓለም ዋንጫ ለሚሳተፈው ቡድን ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት የሚጠበቀው አችራፍ ቤንቻርኪን ጨምሮ በርካታ ጠንካራ ተጫዋቾች ያቀፈ ብሔራዊ ቡድንም ነው። በፈረንሳዊው አሰልጣኝ ሄርቬ ሬናርድ የሚመሩት የአትላስ አንበሶች በሜዳቸው የአሸናፊነት ዕድላቸውን አሳልፈው እንደማይሰጡም ይጠበቃል።
እስከ አሁን በተካሄዱ ጨዋታዎች 30 ጨዋታዎች በአጠቃላይ 53 ግቦች ከመረብ ያረፉ ሲሆን፤ በየጨዋታው በአማካይ 1 ነጥብ 7 ጎል ሲቆጠር ቆይቷል። በግል የጎል አስቆጣሪነትም የሞሮኮው ተጫዋቾች አዩብ ኤል ካቢ በስሙ ስምንት ግቦችን በማስቆጠር ቀዳሚ ተጫዋች ሆኗል። የሊቢያው ሳለህ አል ጣሂር እና የዛምቢያው አውጉስቲን ሙሌይንጋ ደግሞ ሦስት ሦስት ግቦችን በማስቆጠር በእኩል ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋቾች ሆነዋል።
እ.አ.አ በ2009 የተጀመረውን በአገር ውስጥ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ብቻ በሚያሳትፈው ውድድር (ቻን) በማዘጋጀት ቅድሚያውን የወሰደችው ኮትዲቯር ስትሆን፤ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ዋንጫውን አንስታለች። ከሁለት ዓመት በኋላ የአስተናጋጅነት ዕድሉን ባገኘችው ሱዳን በተካሄደው ሻምፒዮናም ቱኒዚያ የዋንጫ ባለቤት ሆናለች። ደቡብ አፍሪካ ባስተናገደችው 3ኛው የቻን ውድድር ደግሞ ሊቢያና ጋና በመለያ ምት ሊቢያ ዋንጫውን የግሏ አድርጋለች። ከሁለት ዓመት በፊት በሩዋንዳ በተካሄደው ሻምፒዮናም ዴሞክራቲክ ኮንጎ በድጋሚ ዋንጫ ያነሳች አገር ሆናለች።

ብርሃን ፈይሳ 

Published in ስፖርት
Page 1 of 3

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።