Items filtered by date: Sunday, 04 February 2018

ከሁሉም አቅጣጫ ሙዚቃ ይሰማል፤ ከአንዳንዱ በድምፅ ማጉያ፤ ከሌላው የብዙዎች ድምፅና የሚደለቅ ከበሮ፤ ከወዲያ መለከት ይነፋል። በአገር ባህል ልብስ የደመቁ ቆነጃጅት ይታያሉ። ቴአትር ቤቶች፣ የባህል ማዕከላት፣ ከተለያዩ ክፍለከተሞች የተውጣጡ የባህል ባለሙያዎች፣ የባህል ቡድኖችና ሌሎችም በርካቶች ተጠጋግተው በአንድ አዳራሽ ታድመዋል። 

የትኛውም ድምፅ ማንንም አልረበሸም፤ ይልቁን ፋታ ሲያገኙ አንዳችው የሌላቸውን ለማየት ይንቀሳቀሳሉ። ይህ የሆነው በኤግዚቢሽን ማዕከል ቁጥር አንድ አዳራሽ ውስጥ ነው። በዚህ አዳራሽ ውስጥ «ባህላችን ለሰላምና አንድነታችን» በሚል መሪ ቃል 9ኛው ከተማ አቀፍ የባህል ሳምንት ተከብሯል። ከጥር 25 እስከ ዛሬ ጥር27/2010ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን፤ ከመክፈቻው ጀምሮም ኢትዮጵያን የሚገልጽ ድባብ ተስተውሎበታል።
በመክፈቻ ስነስርዓቱ ወቅት ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረጻዲቅ ሃጎስ፤ የባህል ሳምንቱ የመከበሩን ምክንያት እንዳስረዱት፤ ወጣቱ የኪነጥበብና የስነ-ጥበብ ሙያውን እንዲያሳድግ ለማበረታታት፤ በባህል ዘርፍ የተሠማሩ ተቋማት ሥራቸውን ለማስተዋወቅ፤ የሚሠሩበትን ዕድል ለመፍጠር እንዲሁም በጎ ባህሎችን ለመጠበቅ የሚያስችል ሥራን ለመሥራት ነው።
ግንዛቤ ለመፍጠር ፌስቲቫሉ ዓይነተኛ መንገድ መሆኑንም የጠቀሱት አቶ ገብረጻዲቅ፤ ምክንያቶቹን ለማጠናከር በዝግጅቱ አውደርዕይ፣ ኪነጥበባዊ ውድድሮች፣ የመዝናኛ ዝግጅቶች እና ዓውደ ጥናቶች መካተታቸውን ያስረዳሉ። በዚህም ከ120 በላይ የሚሆኑ ተቋማት የባህል ምርቶቻቸውን ለተመልካች ለማቅረብና ለማስተዋወቅ ተሳታፊ ሆነዋል፤ ቁጥሩም ካለፈው ዓመት በእጥፍ ማደጉን ጠቁመዋል።
አቶ ፍሬዘር ተስፋሁን «ብርሃን ኢትዮጵያ» የተባለ የባህል ማዕከል ዝግጅት አስተባባሪ ናቸው። በዚህ በዓል ላይ ሲሳተፉም የመጀመሪያቸው እንዳልሆነ ያወሳሉ። ማዕከሉ በባህል ዘርፍ መንገደኞች የኢትዮጵያን ገጽታ በአንድ ቦታ እንዲያዩ በማስቻል ብሎም «ኤክስፒርያንስ ኢትዮጵያ» በሚል ስም በኢትዮጵያዊ አኗኗር የሚሠሩትን ባህላዊ ሥራዎች በተግባር በማሳየት ባህልን የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሠሩ ይገልጻሉ።
የባህል ሳምንቱ መዘጋጀቱ የተለያየ የባህል ዘርፍ ላይ የተሠማሩ ባለሙያዎች ተገናኘተው በጋራ የሚሠሩበት ሁኔታ ካለ እንዲያስቡ እንደሚያግዛቸው ይገልጻሉ። ከዚያም ባሻገር በአንድ አዳራሽ መገኘታቸውም ማኅበረሰቡ፣ የመንግሥት አካላት፣ ከባህር ማዶ የመጡ እንግዶችም ጭምር ሥራቸውን እንዲያዩላቸው እንደሚያግዝ ነው እምነታቸውን የገለጹት።
አቶ ግርማ ለገሰ ደግሞ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል አስተዋዋቂ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ማዕከሉ ቅርሶችንና ባህሎችን የማስተዋወቅ ሥራው ቀዳሚ ነው። እንዲህ ያሉ መርሐ ግብሮች የባህል እሴትና መገለጫዎችን እንዲሁም እደ-ጥበቦችን ለኅብረሰተቡ ለማሳየት፣ ኅብረተሰቡም ከማድነቅ አልፎ እንዲንንከባከባቸውና እንዲጠቀምባቸው ለማድረግ ቀላል የማይባል ሚና አላቸው። ጎብኚዎችም ኢትዮጵያን አንድ ቦታ ሆነው ለማየት ይረዳቸዋል፤ ለባህል ዕድገትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመ ጻሕፍት ኤጀንሲ የመዛግብት አገልግሎት አሰጣጥ ባለሙያ የሆኑት አቶ አብይ ብሩክ በበኩላቸው፤ ከቀደመው ዘመን የተገኙ መዛግብትን በዚህ ሳምንት እየተጎበኙ መሆናቸውን ይናገራሉ። «ጣልያን ከወጣ ጀምሮ ያሉ የኢትዮጵያን ጉዳዮች የሚዳስሱ መዛግብት ይገኛሉ። በተለይም የታሪክና የማኅበራዊ ጉዳይ የሚያጠኑ ሰዎች ወደ እኛ መጥተው እነዚህን መዛግብት እያዩ ጥሩ ጥናታዊ ሥራ እንዲሠሩ ያግዛቸዋልም» ይላሉ። የባህል ሳምንቱም ጥናታዊ ጽሑፎችን ለሚሠሩ ሁሉ ብዙ ምንጮች ሊያስገኙ እንደሚችሉ ያመላከታል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በባህል ሳምንቱ በተለይም በዓውደርዕይ ተሳታፊ የሚሆኑት ሁሉ በየራሳቸው እንደተቋማቸውና እንደመጡት ክፍለ ከተማ የዝግጅቱን ጥቅም ሊያስረዱ ይችላሉ። ከዚያም ባሻገር ደግሞ ከአዳራሹ አንድ ጥግ ሆኖ ሁሉን ለሚመለከት ዓይን አዲስ አበባ ሁሉም በአንድ እየኖረ ያደመቃት መሆኗን ይመለከታል ብለዋል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ረመዳን አሸናፊ፤ እሴቶች እንዲበለጽጉና እንዲዳብሩ ማድረግ፤ የህዝቡን መተሳሰብና የአብሮነት ባህል ይበልጥ በማጠናከር ብሎም አንዱ የሌላውን ባህል እንዲያውቅ ግንዛቤ በማስፋት በኩል የበለጠ ሥራ እንደሚፈለግ ይገልጻሉ። ባህልን በጥበብ ሥራዎች የማሳየት ኃላፊነትንም በጋራ ለማስቀጠል ሁሉም ተባብሮ መሥራት እንዳለበትም አሳስበዋል።

ዜና ሐተታ
ሊድያ ተስፋዬ

 

Published in የሀገር ውስጥ

ወይዘሮ ሃቢባ መሃመድ በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ናቸው። ለሰባት ቤተሰባቸው የሚሆን የመሰረታዊ ምግብ ፍጆታዎችን የሚሸምቱት ደግሞ መንግሥት ባመቻቸላቸው መብት ተጠቅመው በአካባቢያቸው ከሚገኘው የህብረት ሥራ ማህበራት ሱቅ ነው። ነገር ግን በተደጋጋሚ ጊዜ የሚፈልጓቸውን እንደ ስኳር፣ ዘይት እና ዱቄት የመሳሰሉትን ለማግኘት በሚጠይቁበት ጊዜ በተደጋጋሚ አልቋል የሚባል መልስ እንደሚሰጣቸው ይናራሉ። በአካባቢያቸው ከንግድ ሱቆች ጋር በማስተሳሰር ሸቀጦቹን እንዲሸምቱ አሰራር ቢመቻችም ባለሱቆቹም በተመሳሳይ ምርቱን ለተወሰኑ ሰዎች በመስጠት አልቆብናል በማለት መብታቸውን እየጣሱባቸው መሆኑን ያስረዳሉ።
የቤተሰባቸውን ምግብ ፍጆታ ለመሸፈንም ከሌሊቱ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ በማህበራቱ ሱቅ በራፍ ላይ ወረፋ የሚጠበቁት ወይዘሮ ሃቢባ፤ ከእርሳቸው በፊት አሥር እና አሥራ አምስት ሰዎች ቀድመው ከተገኙ የማግኘት ዕድላቸው እየተመናመነ እንደሚሄድ ስጋት ይፈጥርባቸዋል። ስጋታቸው የመነጨው ደግሞ ማህበራቱ ምርቶቹን አስገብተው ማከፋፈል በሚጀምሩበት ቀን በሰዓታት ውስጥ አልቋል የሚል የተለመደ መልስ ስለሚሰጡ ነው። ማህበራቱ የሚያመጡትን ምርት በአግባቡ ለህብረተሰቡ ስለማያደርሱ ዜጎች የችግሩ ገፈት ቀማሽ ሆነዋል።
ማህበራቱ ለ15 ቀናት የተመደበው ፍጆታ ስለዘገየብን በዚህ ሳምንት አገልግሎት የለንም ብለው በቀጣዩ ሳምንት ሌላ ምርት ሲያስገቡ ያለፈውን እና ተጓተተ የተባለው ምርት የት እንደገባ ለማወቅ አይቻልም። በመሆኑም መንግሥት ህብረተሰቡ በመሰረታዊ ፍጆታዎች እጥረት እየደረሰበት ያለውን ችግር ተገንዝቦ ጥብቅ ቁጥጥር ሊያደርግና መብታቸውን ሊያስከብርላቸው እንደሚገባ ይገልጻሉ።
«የሸማቾች ማህበራት ላይ የሚደረገው የሂሳብ ኦዲት በወቅቱ ለህዝብ አይገለጽም» የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሸማቾች ማህበር ተወካይ አቶ ብርሃኔ ተድላ ናቸው። በኦዲቱ የተገኙ ጉድለቶች በአግባቡ ይፋ የማይደረግ በመሆኑም የሚወሰዱ እርምጃዎች ደካማ መሆናቸውን 

ይገልጻሉ። ጉድለቶችን አሳውቆ እርምት ቢወሰድ ግን በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ መሻሻል እንዲታይ ይረዳል። እርምጃ መውሰዱ ሸማቹ ህብረተሰብ አስፈላጊውን የመሰረታዊ ፍጆታዎች በሚያስፈልገው ጊዜ እንዲሸምት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ነገር ግን በቂ ማጣራት አድርጎ መፍትሄ መስጠት ካልተቻለ ህብረተሰቡን የሚያሳስበው የመሰረታዊ ፍጆታዎች እጥረት እንዲቀጥል መፍቀድ ይሆናል። በመሆኑም የሸማቾች የህብረት ሥራ ማህበራት ላይ የሚደረገው ክትትል መጠናከር ይኖርበታል የሚል እምነት አላቸው።
በፌዴራል የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን የኮርፖሬት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ግርማ አለማር በበኩላቸው፤ ለህብረተሰቡ የሚቀርቡት መሰረታዊ የምግብ ፍጆታዎች ላይ መንግሥት ከፍተኛ ድጎማ ያደርግባቸዋል። በመሆኑም ምርቶቹ ለታለመላቸው ግብ እንዲውሉ የመከታተልና የመቆጣጠር ሥራው ከመንግሥት በተጨማሪ የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት መሆን ይገባዋል። የግል ጥቅማቸውን ለማካበት የሚፈልጉ የማህበራት ሠራተኞች በሚፈጽሙት ህገወጥ ተግባር ከሸቀጦቹ ህጋዊ የስርጭት መስመር ውጪ ለሚገኙ ነጋዴዎች ምርቶችን ያቀርባሉ። ችግሩም የምርት እጥረት እንዲፈጠር በማድረግ በአዲስ አበባ እና በክልሎች ላይ የሚገኙ ሸማቾች ላይ ምሬት ይፈጥራል።
እንደ አቶ ግርማ ማብራሪያ፤ ህገወጦቹም ከአብዛኛው ሸማች ህብረተሰብ ጋር ሲነጻጸሩ በቁጥር አነስተኛ በመሆናቸው ከተቆጣጣሪ አካላት በተጨማሪ ህብረተሰቡ «ለእኔ የመጣውን ፍጆታ ያለአግባብ ተሰራጭቷል» በሚል መንፈስ ማንኛውንም ጥፋተኛ መከላከል መቻል ይኖርበታል።
በህገወጥ መንገድ ሲከማች፣ ሲጓጓዝ እና ሲሸጥ የተገኘ ምርትም በሚገኝበት ጊዜ በአካባቢው ለሚገኙ ንግድ ቢሮዎች እና ለህግ አካላት ጥቆማ በመስጠት ማጋለጥ ያስፈልጋል። ችግሮች በተከሰተባቸው የህብረት ሥራ ማህበራት ሱቆች እና ህገወጦች ላይም ከፌዴራል ዓቃቢ ህግ እና ከንግድ ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት ከዚህ ቀደም አስፈላጊው ማጣራት እና እርምጃ ሲወሰድ ቆይቷል። በመሆኑም ህገወጦች የሚፈጥሩትን የመሰረታዊ ፍጆታ እጥረት ለመከላከል በጋራ መስራት እንደሚገባ ያሳስባሉ።
«በአዲስ አበባ የመሰረታዊ ፍጆታዎችን ለማከፋፈል የወጣው አዋጅ በእራሱ ችግር አለው» የሚሉት ደግሞ የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ንግድ ጽህፈት ቤት የንግድ ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ መዝገበ ሞላ ናቸው። እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ በከተማዋ የመሰረታዊ ሸቀጥ መመሪያ መሰረት ማንኛውም ሬስቶራንት እና ካፍቴሪያ ስድስት ኩንታል ስኳር የመውሰድ መብት ይሰጣል። አብዛኛዎቹ ሬስቶራንቶች ደግሞ ምግብና አልኮል መጠጥ የሚያቀርቡ በመሆናቸው ስኳርን እንደ ግብዓት አይጠቀሙም። በመሆኑም ክፍለ ከተማው ላይ የሻይ ማሽን የሌላቸው እና ስኳርን ለግብአትነት የማይጠቀሙ የንግድ ድርጅቶች ኮታውን እንዳያገኙ አዲስ አሰራር ተዘርግቷል። አዋጁ የስኳር እጥረት እንዲፈጠር በር የከፈተ ቢሆንም ካለው ችግር አኳያ አሰራሩ እንዲለመድ እየተደረገ ይገኛል። ዘይትንም በተመለከተ የማያስፈልገውም የሚያስፈልገውም እንዲወስድ ይደረጋል። በመሆኑም ለመሰረታዊው ፍጆታ እጥረት የሚዳርገውን አዋጅ በማሻሻል ምክንያታዊ የሆነ ክፍፍልን መተግበር እንደሚገባ ይናገራሉ።
በሌላ በኩል የፍጆታ እጥረት እንዲፈጠር ከነጋዴዎች ጋር ያለአግባብ የሚተሳሰሩ የሸማች ማህበራት መኖራቸው ችግሩን አሳሳቢ እንዳደረገው አቶ መዝገበ ይናገራሉ። በተለያዩ አካባቢዎች በአስገነቧቸው መጋዘኖች ምርቶቹን አከማችተው የተገኙ እና በተሽከርካሪዎች ሲያንቀሳቅሱ የተያዙ ህገወጦችም እየተጋለጡ ናቸው። በአብዛኛው በሽፍን ሚኒባስ ተሽከርካሪዎች ሲንቀሳቀሱ የሚገኙ ህገወጥ ሸቀጦችም ምንጫቸው ሲጣራ የሸማች ማህበራት ሱቆች ላይ ይወድቃል።
በተለይ ስኳር እና ዘይት ምርቶችን ለህገወጥ ነጋዴዎች በማቅረብ የሚሰሩ እና ተቀባይ ግለሰቦች ላይ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ ቢሆንም አሁንም ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር አልተቻለም። ባለፉት ስድስት ወራት በክፍለ ከተማው ብቻ ሁለት መቶ ሺህ ብር የሚያወጡ ምርቶች በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረግ ተችሏል። በመሆኑም የመሰረታዊ ፍጆታዎችን እጥረት ለመቀነስ ህጉን ከማስተካከል በተጨማሪ ከህብረተሰቡ በተገኘው አጋጣሚ ሆኑ ህገወጦቹን ማጋለጥ ይጠበቅበታል። ለማጋለጡም ተግባር 8588 ነጻ የስል መስመር መጠቀም እንደሚቻል ጠቁመዋል።

 

ዜና ሐተታ
ጌትነት ተስፋማርያም

 

 

Published in የሀገር ውስጥ

ወደ አረብ አገራት ለሥራ በሚሄዱ የቤት ሠራተኞች ላይ የሚደርሰው ችግር ዘግናኝ እንደነበር በተለያየ አጋጣሚ ይነገራል። የሰሩበትን ገንዘብ ከመከልከል እስከ አካል ጉዳትና ህልፈተ ሕይወት እንደሚደርስባቸው የዓይን እማኞች ተናግረዋል። አገራቱም ቢሆኑ ‹‹ውጡልን›› በማለት እንግልትና የስነ ልቦና ቀውስ ሲያደርጉ ተስተውሏል። ይህንን ተከትሎም በ2001ዓ.ም የውጭ አገር የሥራ ሥምሪትን የሚፈቅድ አዋጅ ወጥቶ እንደነበር ይታወሳል። ይሁን እንጂ አዋጁ የህግ ክፍተት አለበት በማለት መንግሥት በ2006 ዓ.ም እገዳ ጥሎበታል።
በመሀሉም በህገ ወጥ መንገድ ሠራተኞች ሲሄዱ ቢቆዩም የሚደርስባቸውን እንግልት ለመቀነስ የበፊቱ አዋጅ 632/2001 እንዲሻሻል ተደርጎ በ2008 ዓ.ም የማሻሻያ አዋጅ ፀድቋል። ተጥሎ የነበረው የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት እገዳም የአዲሱን አዋጅ 923/2008 መውጣት ተከትሎ ከጥር 22 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ተነስቷል፡፡ ለመሆኑ የተሻሻለው አዲሱ የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት አዋጅ ለሠራተኞች ምን ያስገኝ ይሆን? አሰሪዎችና ኤጀንሲዎችስ ምን ይጠበቅባቸዋል?
በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋናው አድማሱ እንደሚሉት፤ ቀደም ሲል የነበረው አዋጅ ውስብስብና ግልጽ ያልሆኑ ደንቦች ስለነበሩበት ነው በ2006 ዓ.ም እንዲቆም የተደረገው።  አሁን የተሻሻለው አዋጅ ደግሞ ለሠራተኞች ደህንነት ሲባል ከላኪ ኤጀንሲዎችና ከአሰሪዎች የሚጠበቅ ባቸውን ግዴታ በግልጽ ያስቀመጠ ነው። በአዋጁ ውስጥ አዳዲስ አንቀጾች ተካተዋል። አሰሪዎች የሚፈልጉትን ሠራተኛ መስፈርትም በግልጽ ያስቀመጠና ከመሄዳቸው በፊት ሥልጠና እንዲወስዱም ያደርጋል። አንድ ለሥራ የሚሄድ ሰው ማሟላት ባለበት መስፈርት ተመዝኖ ነው እንዲጓዝ የሚደረገው።
እንደ አምባሳደር ምስጋናው ገለጻ፤ አዲስ በተሻሻለው አዋጅ መሰረት አንድ ወደ ውጭ አገር ለሥራ የሚሄድ ሠራተኛ ቢያንስ ስምንተኛ ክፍልን የጨረሰ መሆን አለበት። አዋጁን ተከትለው በሚወጡ ደንብና መመሪያዎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ይደረግባቸዋል። የሚሰጡት ሥልጠናዎችም ተከታታይነት ያላቸው ይሆናሉ። ለዚህም ከክልሎችና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር እየተሰራ ነው። እስካሁንም ከአሥር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር ሥራ ተጀምሯል። ወደ ውጭ አገራት ለሥራ ከመሄዳቸው በፊት ለሚሰጠው ሥልጠና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተዘጋጅተዋል። ሠራተኞቹ ሥልጠናቸውን ጨርሰው ለሥራ በሚሄዱባቸው አገራትም ክትትል የሚያደር ጉላቸው(ሌበር አታሸ) ተመቻችቷል።
ለሠራተኞቹ ለሚደረገው የጤና ምርመራም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተለዩ 66 የጤና ተቋማት መዘጋጀታቸውን የሚናገሩት አምባሳደር ምስጋናው፤ ለሠራተኞቹ ሥልጠና መስጠት ብቻ ሳይሆን የወሰዱትን ሥልጠና በትክክል መተግበር ይችላሉ አይችሉም? የሚለውን ለመለየት ከብቃት ማረጋገጫ ኤጀንሲ ጋር በመሆን የብቃት መመዘኛም ይሰጣቸዋል፤ የብቃት ማረጋገጫም እንደሚያገኙ ያስረዳሉ።
አገናኝ ኤጀንሲዎች በአዲሱ የተሻሻለው አዋጅ መሰረት የተመረጡ መሆናቸውን የሚጠቁሙት አምባሳደር ምስጋናው፤ የሚፈለገውን መስፈርት አሟልተው የተገኙት ብቻ ናቸው ፈቃድ የተሰጣቸው። 980 ኤጀንሲዎች ጥያቄ አቅርበው ፈቃድ ያገኙትም 20ዎቹ ብቻ መሆናቸውን ተናግረዋል። ሠራተኞቹም የትኞቹ አገራት ሄደው መሥራት እንዳለባቸው ተለይተው ከአገራቱ ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት ተደርጓል። እነዚህም አገራት ኩዌት፣ ኳታር እና ጆርዳን መሆናቸውንም ጠቁመዋል። እንደ አረብ ኢሚሬት እና ባህሬን ካሉት አገራት ጋር ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት በሂደት ላይ መሆኑን አስረድተውም ፈቃድ ያገኙት ኤጀንሲዎች ስምምነት ከተደረገባቸው አገራት ውጭ መላክ እንደማይችሉም አስገንዝበዋል።
20 ኤጀንሲዎች ብቻ መመረጣቸው በቂ ሆኖ ሳይሆን በጊዜው መስፈርቱን አሟልተው የተገኙ ስለሆነ ነው የሚሉት ደግሞ በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ አገር ሥራ ስምሪት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ብርሃኑ አበራ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ዋናው ነገር ብዛታቸው ሳይሆን የሚፈለገውን መስፈርት አሟልተው መገኘታቸው ነው። ይሁንና በቀጣይ በሂደት ላይ ያሉትን ጨምሮ አዲስ አመልካቾችም ካሉ ማመልከት ይችላሉ። ይሁን እንጂ ከዚህ በፊት የነበሩት ኤጀንሲዎችን በተመለከተ ከሦስት በላይ እግድ ያለበት ኤጀንሲ መግባት አይችልም። በአሁኑ አዋጅ 923/2008 ፈቃድ የተሰጣቸው ከሦስት በላይ እግድ የሌለባቸው ብቻ ናቸው እንዲሳተፉ የሚፈቀደው። 97 ኤጀንሲያዎች ከሦስት በላይ እግድ ስለነበረባቸው ፈቃድ ተከልክለዋል። ከእነዚህ ውጭ ሌሎቹ መስፈርታቸውን አሟልተው እንደገና መቀላቀል ይችላሉ፡፡
እንደ አቶ ብርሃኑ ገለጻ፤ እስካሁን ወደ አረብ አገራት ይሄዱ የነበሩ ሠራተኞች ማንበብና መጻፍ እንኳን የማይችሉም ናቸው። በአዋጁ ላይ ቢያንስ ስምንተኛ ክፍል የጨረሱ መሆን እንዳለበት መደረጉ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ውጭ እንዳልሆነ ያስረዳል። በአገሪቱ ውስጥ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት ከዘጠና በመቶ በላይ ደርሷል። ስለዚህም ማንበብ፣ መጻፍ ሳይችሉ የሚሄዱት ከፍተኛ የሆነ የስነ ልቦና ቀውስ ሲደርስባቸው ነበር። የዕቃዎችን ስም መለየት አይችሉም ነበር። ስለዚህም ችግሩን ለመፍታት ስልጠና እንዲመቻች ተደርጓል።
በህጋዊ መንገድ ከአሰሪዎች ጋር በሚደረግ ስምምነት ደግሞ ከሠራተኛው የሚፈልጉት መስፈርት የተሟላ መሆን እንዳለበት ስለታመነ ስምንተኛ ክፍል ያልጨረሰ እንዳይጓዝ ተደርጓል የሚሉት አቶ ብርሃኑ፤ ከመሄዳቸው በፊት ለሚሰጣቸው ሥልጠና ማንበብና መጻፍ የሚችሉ መሆን አለባቸው። ሥልጠና መሰጠቱ በራስ መተማመን እንዲኖራቸውና ከሌሎች አገራት ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፤ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸውም 40 ያህል የቴክኒክና ሙያ ተቋማት እንደተዘጋጀላቸው አስረድተዋል።
በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰው ኃይል ጥናትና ስምሪት ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አበበ ኃይሌ በበኩላቸው እንዳሉት፤ መንግሥት የውጭ አገር ሥራ ስምሪትን አያበረታታም፤ ዳሩ ግን ‹‹ሄጄ መስራት እፈልጋለሁ›› ለሚሉ በህገ ወጥ መንገድ ከሚሄዱ ይልቅ ህጋዊ መሆን ስላለባቸው አዋጁን በማሻሻል የተጣለውን እገዳ ማንሳት እንዳስፈለገ ይናገራሉ። የበፊቱ አዋጅ ክፍተቶች ስለነበሩበት ሠራተኞቹን ህገወጥ ሥራዎች ሁሉ ያሰሯቸው ነበር፤ አሁን በተሻሻለው ስምምነት ግን የተጠቀሱ ሥራዎችን ብቻ እንዲሰሩ ነው የሚደረገው። ይህም ለሠራተኛው ደህንነት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። ወደ ውጭ አገራት ለሥራ የሚሄዱት በደላላ ግፊት ሳይሆን ግልጽ በሆነ አሰራር ይሆናል። አሰሪዎችም የሚጠበቅባቸውን ግዴታ ተለይቶ አስቀምጧል።
አሰሪዎች ከሠራተኞች ለሚፈልጉት መስፈርት ሥልጠና ይሰጣል የሚሉት አቶ አበበ፤ በአማርኛና በአረብኛ ቋንቋ ማስተማሪያ ቡክሌቶች እንደተዘጋጁ፣ ሠራተኞች በአሰሪዎች እንግልት እንዳይደርስባቸው፣ ደመወዝ እንዳይከለከሉና የእረፍት ጊዜ እንዲኖራቸው በአዋጁ ላይ እንደተቀመጠ ይገልጻሉ። ወደ አረብ አገራት ለሥራ ለሚሄዱ ሠራተኞችም የሚሰጡ ሥልጠናዎች በሦስት ጉዳዮች ላይ ያተኩሮ ናቸው። በቤት ውስጥ መንከባከብ፤ ሕጻናትን፣ አዛውንትንና ታማሚዎች ሲሆኑ፤ በቤት ውስጥ አገልግሎት ደግሞ ፅዳት፣ አትክልትና ልምዱ ካላቸው ሹፍርናን ይሰለጥናሉ። እንዲሁም በቤት ውስጥ እርዳታ ደግሞ ምግብ ማብሰልና ልብስ ማጠብ የመሳሰሉት በሥልጠናው ተካቶ እንደሚሰጣቸው ጠቁመዋል።  

ዜና ሐተታ
ዋለልኝ አየለ

Published in የሀገር ውስጥ

ሰሞኑን በአፍሪካ ህብረት የተሰበሰቡ የአህጉሪቷ መሪዎች የአፍሪካ ነጻ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ስምምነት /The Single African Air Transport Market (SAATM)/ ወደ ትግበራ እንዲያመራ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። 23 የአፍሪካ አገራት የተፈራረሙት የትግበራ ስምምነት ለኢትዮጵያ ምን ፋይዳ ሊኖረው ይችላል? በሚለው ጉዳይ ላይ የዘርፉ ተዋናዮች ኃሳባቸውን ይገልጻሉ።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ምክትል ፕሬዚዳንት የስትራቴጂክ ፕላኒንግ እና አላያንስ አቶ ሄኖክ ተፈራ እንደሚገልጹት፤ በአፍሪካ ህብረት ደረጃ 55 አባል አገራት አሉ። እያንዳንዱ አገር ከዚህ ቀደም የአየር በረራ የሚያካሂደው ማን፣ መቼ፣ እንዴት ይበራል? የሚለውን አገራት በሚያደርጉት በሁለትዮሽ ስምምነት ላይ መሰረት አድርጎ በሚወሰድ ውሳኔ መሰረት ነው። ይህ አይነቱ አሰራር የአህጉሪቷን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል። ሰሞኑን በተደረሰው የትግበራ ስምምነት ደግሞ በአገራቱ ስም የተመዘገቡ የአየር መንገድ አውሮፕላኖች በአየር ክልላቸው ውስጥ ያለ ክልከላ እና ገደብ እንዲበሩ ፍቃድ ይሰጣል። የሁለት አገራት አየር ተቆጣጣሪዎች ለእያንዳንዱ በረራ ከሚሰጡት ፍቃድ ውጪም የአገራቱ አውሮፕላኖች መብረር እና ማረፍ እንዲችሉ ዕድል ይፈጥራል። ነገር ግን በወቅቱ ኢትዮጵያ ለጉዳዩ  ከፍተኛ ትኩረት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት የትራንስፖርት ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ እንደሚገልጹት ደግሞ፤ ስምምነቱ የአፍሪካን አየር ትራንስፖርት ገበያ በዘርፉ ለተሰማሩ አፍሪካዊ ተቋማት ክፍት ለማድረግ ያለመ ነው። ስምምነቱ በአፍሪካ አገራት መካከል ነጻ የአየር ትራንስፖርት የገበያው አማካኝነት ትስስራቸው እንዲጠናከር ይረዳል። በአገራቱ መካከል ክልከላዎች ሳይኖሩ በአየር ክልላቸው ውስጥ የገባ የስምምነቱ አካል አገር አየር መንገድ አውሮፕላኖች በአየር ክልላቸው እንዲገቡ እና እንዲወጡ ፈቃድ ይሰጣል።
አሰራሩን በዓለም ላይ የሚገኙ ከአፍሪካ ውጪ ያሉ አህጉራት ተግባራዊ እያደረጉት ቢገኝም አፍሪካ ላይ ተግባራዊ ሳይደረግ እንደቆየ የሚያስረዱት አማካሪው፤ እ.አ.አ2015 ላይ11 አገራት የነጻ የአየር በረራውን ጥቅም በመረዳታቸው በጋራ ለመስራት ቢስማሙም ወደ ሥራ መግባት አልቻሉም ነበር።
በመስጠት የማነሳሳቱን ሥራ አከናውናለች። በዚህም በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተውን አማራጭ የተቀበሉ አገራት አሁን ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ 23 መድረሳቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው እንዳብራሩት፤ የአፍሪካ አገራት አየር መንገዶቻቸው መፍቀዳቸው እንደ አገር ለኢትዮጵያ አዋጭ ነው። ምክንያቱም ወደተለያዩ አገራት ለመብረር የሚወሰደውን የፍቃድ የስምምነት ሂደት የሚያስቀር በመሆኑ የአየር ትራንስፖርቱን የበለጠ ያቀላጥፈዋል። «የአፍሪካን ገበያ ለአህጉሪቷ አየር መንገድ» የሚል ዓላማ ስላለው ኢትዮጵያ በአፍሪካ አየር በረራ ላይ ያላትን ድርሻ ለማስፋት ይረዳታል። ከአንዱ የአፍሪካ አገር አየር መንገድ ወደ ሌላ አገር ለመብረር ፍቃድ መጠየቅ ያስፈልግ የነበረውን አሰራር በማስቀረት ያለምንም ገደብ ወደ የትኛውም የአፍሪካ ሀገር ለመብረር እድል ይፈጥርላታል። የኢትዮጵያ አየር መንገድም በአስፈለገው አቅጣጫ መስመሩን ቀይሶ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር ያስችለዋል።
«የአፍሪካ አገራት ወደ ሌሎች አህጉራት በብዛት ቢበሩም በመካከላቸው ያለው በረራ ዝቅተኛ ነው» የሚሉት አቶ ሄኖክ፤ ስምምነቱ በአገራቱ መካከል ያለውን የአየር በረራ ቁጥር እንዲጨምር እድል የሚሰጥ በመሆኑ በመካከላቸው የቱሪዝም፣ የኢንቨስትመንት፣ የንግድ እና የማህበራዊ ትስስሩን ያጠናክረዋል። በዚህም በረራዎች ሲበራከቱ የአቪዬሽን ዘርፉ እንዲያድግ እና በአገራቱ ውስጥ የስራ እድል እንዲስፋፋ በር ከፋች ይሆናል ይላሉ። ኢትዮጵያም በትግበራ ስምምነቱ የተካተተች በመሆኗ በስምምነቱ በተጠቃለሉ አገራት የሚያደርገው በረራ ቁጥሩ እንዲጨምር እና በርካታ ሰዎችን እንዲያመላልሱ እንደሚያግዘው ይገልጻሉ።
የአፍሪካ አየር መንገዶች መነሻ መስመራቸውን ከሌላኛው የአፍሪካ አገር አድርገው እንዲሰይሙ ይረዳል። ለአብነት ወደ ፊት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፓሪስ መበረር ቢፈልግ የግድ በአዲስ አበባ አድርጎ ሳይሆን በቻድ ወይም በሌላ የአፍሪካ አገር ኢንተርናሽናል አየር ማረፊያ በመጠቀም ሊሆን እንደሚችል የሚናገሩት አቶ ሄኖክ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአህጉሪቷ ያልነበረው የገበያ እድል በስፋት እንዲጠቀም በር ከፋች መሆኑን ይገልጻሉ።
እንደ አማካሪው ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያ ቀጥታ በረራዎችን በአፍሪካ አገራት በኩል ለመተግበር አይነተኛ መንገድ ነው። ለአብነት በፈረንሳይ አድርጎ አልጀሪያ የሚሄደውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በስምምነቱ መሰረት ቀጥታ አልጀሪያ እንዲሄድ እድል ይፈጠራል። አሰራሩ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አየር መንገዶች ወደተለያዩ የአፍሪካ አገራት ለመብረር ሲፈለጉ በቀላሉ ያለክልከላ ለመሄድ ያግዛቸዋል። በመሆኑም የአየር በረራ ፍቃድ አሰራር መዳረሻዎችን ለማስፋት እና በርካታ ተጓዦችን ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገራት ለማመላለስ አመቺ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አድማሱን በማስፈት ገበያውንም ለመጨመር ያስችለዋል። ይህ ማለት ደግሞ በኢትዮጵያ እና በሌሎቹ የአፍሪካ አገራት መካከል የሚደረገው በረራ አማካኝነት የንግድ እና የኢኮኖሚ ትስስሮች እንዲጠናከሩ አይነተኛ መንገድ ይፈጥራል። የኢትዮጵያ አምራች እና ነጋዴዎች በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ምርቶቻቸውን እንዲያከፋፍሉ በማድረግ የወጪ ንግድ ላይ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ይሆናል።
እንደ ኮሎኔል ወሰንየለህ ገለጻ፤ በኢትዮጵያ በኩል የአየር በረራ ደህንነቱ በአስተማማኝ ደረጃ ላይ ይገኛል። ከእያንዳንዳቸው አገራት በአንድ ጊዜ ሁለት በረራዎች ወደ ኢትዮጵያ ቢደረጉ እንኳን ምንም ችግር ሳይፈጠር ማስተናገድ የሚቻልበት አቅም አለ። በመሆኑም ያለክልከላ የሚበሩ አውሮፕላኖች ስለሚኖሩ በብቻ የሚኖረውን ስጋት በመከላከል ረገድ ያለው ዕድል አስተማማኝ በማድረግ ችግሩ ይፈታል። ኢትዮጵያ የነጻ አየር ገበያውን መጠቀም የሚያስችል አቅም አላት። ነገር ግን የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ተቋም በሚፈልገው እና ዘመኑ እየተራቀቀ በሄደበት ልክ የደህንነት ቁጥጥርን የተከተሉ ስራዎች ወደ ፊት አጠናክሮ መቀጠል ይገባል። አሁን ላይ ደህንነቱ አስተማማኝ ነው ተብሎ የሚተው ባለመሆኑም ስራውን በተከታታይ መስራት ይጠበቃል።
እ.አ.አ በ1994 በኮትዲቯር ያማሶኡክሮ ከተማ የአፍሪካ ነጻ የአየር ትራንስፖርት ንግድ እንዲተገበር ውሳኔ ተላልፏል። ነገር ግን ውሳኔው ተግባራዊ ሳይደረግ ቆይቷል። ከሦስት ዓመታት በፊት ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 አገራት ወደ ትግበራ ለመግባት ስምምነት አድርገው ነበር። በቅርቡ በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ላይ 23 አገራት ወደ ትግበራ የሚያስገባቸውን ስምምነት አድርገዋል። በስምምነቱ ኢትዮጵያ፣ ናይጀሪያ፣ ግብጽ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ጋና እና ኬንያ እንዲሁም ሩዋንዳ ተካተውበታል። አገራቱ የአህጉሪቱን 80 በመቶ የአየር ትራንስፖርት ድርሻ የሚይዙ በመሆኑ የሥራ እድል በመፍጠር እና የእርስ በእርስ ግንኙነት በማጠናከር ረገድ በበጎነቱ ታይቷል።
ኮሎኔል ወሰንየለህ በበኩላቸው፤ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመሳሰሉ ጠንካራ ተቋማት በርካታ አውሮፕላኖችን አሰማርቶ የመዳረሻ አድማስን ለማስፋት እድል እንዳለው ይገልጻሉ። ነገር ግን በቀጣይ ጊዜያት የስምምነቱ አካላት የሚሆኑ ተጨማሪ አገራትን ማካተቱ አይነተኛ ሚና ይኖረዋል። የአገራቱ ቁጥር በጨመረ ቁጥጥር በረራ የሚደረግባቸውም ቦታዎች በዛው ልክ ማስፋት ያስችላል። በመሆኑም ቀሪዎቹ አገራት እንዲካተቱ ጥረት ማድረግ በቀጣይ እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ።
አማካሪው የኮሎኔል ወሰንየለህን ተጨማሪ አገራትን ማካተት ይጠቅማል የሚለውን ሃሳብ ይደግፋሉ። በቀጣይ ቀሪዎቹ ከሰላሳ በላይ የሆኑት የአፍሪካ አገራት በስምምነቱ እንዲካተቱ ማድረግ ለውጤታማነቱ አስፈላጊ ነው። እያንዳንዱ አገር የአንድ አፍሪካ አየር ትራንስፖርት ስምምነት ትግበራ ላይ እንዲሳተፉ ማሳመን ያስፈልጋል። ቀሪዎቹ አገራት ለትግበራው ተሳታፊ እንዲሆኑ አሁን ላይ ስምምነቱ ውስጥ የገቡ አገራት በአሰራሩ ተጠቃሚ መሆናቸውን በተግባር ማሳየት አለባቸው። ሂደቶቹንም ተከተሎ ነጻ የአየር ገበያውን በመጠቀም ወደ ንግድ ትስስሩ መግባት ያስፈልጋል። ነገር ግን ሁሉም አገራት ስምምነቱ ውስጥ መካተት በአህጉሩ ውስጥ ያለምንም ገደብ ለመብረር የሚያስችለውን እድል ይፈጥራል ቢባልም የተወሰኑ አገራት ስምምነቱን ባይፈልጉት የኢትዮጵያን የአየር ገበያ ድርሻን የሚነካ ችግር አይሆንም።
እንደ አቶ ሄኖክ ገለጻ ከሆነ፤ ስምምነቱ ወደ ትግበራ ሳይገባ በመቆየቱ የአፍሪካን የአየር ትራንስፖርት ገበያ ወደ ኋላ አስቀርቶታል። በመሆኑም ከስምምነቱ የሚገኘውን ጥቅም ለመቋደስ እንዲቻል በፍጥነት ወደ ትግበራ መግባት እና ጠንካራ ተቆጣጣሪ ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ይሁንና በፍጥነት ወደ ትግበራ ካልተገባ እና የነጻ በረራው አሰራሩን መጠቀም ካልተቻለ ከስምምነቱ የሚገኘውን እድል በአግባቡ እና በጊዜው ለመጠቀም እክል ይፈጠራል። ስምምነቱ በጎ ተግባር በመሆኑ ትግበራውን ማፋጠን ደግሞ ቀሪ ሥራ መሆን እንዳለበት አብራርተዋል። 

 ዜና ትንታኔ
ጌትነት ተሰፋማርያም

Published in የሀገር ውስጥ
Sunday, 04 February 2018 00:00

ሜዳው ሰው አብቅሏል

ከሳምንት በፊት ነው። ከጓደኛዬ ጋር ከስራ በኋላ በእግራችን እየተጓዝን ነው። የእግር ጉዞ ለጤናም ለጨዋታም ይጠቅማል አይደል የሚባለው። በአጋጣሚ ለብዙ ጊዜ እየተመለከትኩት ያላስተዋልኩትን አንድ የእግር ኳስ ሜዳ ጋር ስደርስ ድንገት ቀልቤን የሳበው ነገር አጋጠመኝ እና ቆም አልኩ። ከ30 የሚበልጡ ሰዎች ሙሉ የእግር ኳስ ትጥቅ ለብሰው ልምምድ ያደርጋሉ። ታዲያ ይሄ ምን ይገርማል? ትሉ ይሆናል። እኔን የገረመኝ ሰዎቹ ያላቸው ተክለ ሰውነት አንድ እግር ለኳስ ተጫዋች ሊኖረው የሚገባ አቋም ባለመሆኑ ነበር። ቢሆንስ ታዲያ ለጤናቸው እየሰሩ ነዋ! ትሉ ይሆናል። እውነት ነው ለጤናቸው ነው የሚሰሩት። ግን ስነምግባራቸው እና ያላቸው ሞራል ከማስገረምም አልፎ ቀልብን ይስብ ነበር።
ልምምዳቸውን ከመመልከት ባለፈ የቡድን መሪያቸውን ጠጋ ብዬ አናገርኩት። የእግር ኳስ ጤና ማህበር እንደሆነ አጫወተኝ። ሜዳው ቀበና አካባቢ የሚገኘው «የቤሌር እግር ካስ ሜዳ ይባላል፤ ይህ ስፍራ አንተ ከምታስበው በላይ ታዋቂና አንጋፋ እግር ኳስ ተጫዋቾችን አፍርቷል። ነገር ግን ለበርካታ ጊዜያት ተረስቶ የቆሻሻ መጣያ ሆኖ ነበር። ታዳጊዎችም ማዘውተሪያ ስፍራ አልነበራቸውም» ብሎኝ ላለፉት አራት አመታት ሜዳው የነበረውን የቀድሞ ስም ለመመለስ፣ ማህበራቸውም ጤናን መሰረት አድርጎ ስፖርትን ከማበረታታት ባለፈ ለታዳጊ ወጣቶች ተስፋ የሚፈነጥቁ ስራዎች ለመስራት እየጣረ መሆኑን ነገረኝ። በሰፊው ለመጨዋወት ተቀጣጥረን በሳምንቱ ተገናኘን።
ዳዊት ግርማ ይባላል። በቀበና 15 ሜዳና አካባቢ እየተባለ በሚጠራው ሰፈር ነዋሪ ነው። ከልጅነቱ ጀምሮ በአካባቢው «ቤሌር» እየተባለ በሚታወቀው ሜዳ ከጓደኞቹ ጋር ኳስን እያንከባለለ ነው ያደገው። በግል ስራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው ጎልማሳ ከስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እግር ኳስን በተለየ ሁኔታ ይወዳል። በአሁኑ ወቅት ከአብሮ አደጎቹ ጋር በጋራ በመሆን «የአስራ አምስት ሜዳና አካባቢው የጤና እግር ኳስ ማህበር» መስርተዋል። እርሱም የማህበሩ ሰብሳቢ በመሆን ያገለግላል።
«የእግር ኳስ ማህበሩ ከተመሰረተ አራት አመታትን አስቆጠሯል» በማለት በዋናነት ምስረታው በርካታ አላማዎችን አንግቦ እንደሆነ የሚናገረው ዳዊት፤ የቤሌር ሜዳ ከዚህ ቀደም ለኢትዮጰያ እግር ኳስ ያበረከተው አስተዋፆ ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራል። ሆኖም ለብዙ አመታት «የቆሻሻ መጣያ እና መፀዳጃ» ሆኖ የአካባቢውን ሰው ለጤና ችግር ሲያጋልጠው ቆይቷል። የአካባቢው አብሮ አደጎችም ይህንን በመገንዘብ የቀድሞውን ዝና ለመመለስ፣ ህብረተሰቡንም ለጤና ችግር የሚያጋልጡ ቆሻሻዎችን ለማስወገድ እና ሌሎች በጎ አላማዎችን ለመስራት በአንድ ጥላ ስር ተሰባስበዋል። በሳምንት ሶስት ጊዜ ልምምድ እንዲሁም በየጊዜው የተለያዩ ውድድሮችን በማድረግ ጤናቸውን ይጠብቃሉ።
«አሁን በራሳችን ጥረት እና በአንዳንድ በጎ ፍቃደኛ ባለሀብቶች የሜዳውን ፅዳት መጠበቅ እና ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ለማድረግ ጥረት አድርገናል» የሚለው የማህበሩ ሰብሳቢ አሁንም ድረስ በስፍራው ላይ መሰራት ያለባቸው ቀሪ ተግባራት መኖራቸውን ይናገራል።
የአዲስ አበባ ጤና ስፖርት ማህበር የሚመራቸው በከተማዋ የሚገኙ ከ30 በላይ ማህበራት አሉ። ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ጤናን መጠበቅ እና ማህበራዊ ግንኙነትን ማጠናከርን ታሳቢ አድርገው የተመሰረቱ ናቸው። የአስራ አምስት ሜዳና አካባቢው የጤና እግር ኳስ ማህበርም ከነዚህ መካከል የሚመደብ ነው። ከሌሎች ማህበራት ልዩ የሚያደርገው ግን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ጉልህ ስፍራ ያላቸው ተጫዋቾችን ማፍራት የቻለው «የቤሌር ሜዳ» ቀድሞ የነበረውን ስም እና ዝና በመመለስ አሁንም ብቃት ያላቸው ተጫዋቾች እንዲያፈራ ለማስቻል በሚያደርገው ብርቱ ጥረት ነው።
የማህበሩ አባላት ከልጅነታቸው ጀምሮ በዚህ ሜዳ ላይ እየተፎካከሩ አንዳንዴም እየተጣሉ በአንዳንድ ምክንያት ሲለያዩ ደግሞ እየተነፋፈቁ ለረጅም አመታት አሳልፈዋል። ከሁሉም ከሁሉም ይህን ማህበር በቁርጠኝነት መስርተው የሜዳውን የቀድሞ ዝና ከዚያም አልፎ የአብሮ አደግነታቸውን ፍቅር ለመመለስ ያነሳሳቸው የአንድ ጓደኛቸው ሞት ነበር። የዚህ ሰው ሞት ከምንም ነገር በላይ ያስቆጫቸው ደግሞ በህክምና መዳን በሚችል ህመም ደጋፊ በማጣቱ ብቻ በመሞቱ ነበር። ክስተቱ የእነርሱ አለመሰባሰብና በአንድነት ያለመረዳዳት ምን ያክል ጉዳት እንዳለው በይበልጥ አስረድቷቸዋል።
አባላቱ «እግር ኳስ ሁላችንንም በአንድነት የማሰባሰብ እና እንድንደጋገፍ የማድረግ ሀይል አለው» የሚል እሳቤ አላቸው። ተዳፍኖ የቆየውን የቤሌር ሜዳ በድጋሚ እንዲያንሰራራ ከማድረግ እና ተስፋ ያላቸው እግር ኳስ ተጫዋቾችን ለአገሪቷ ከማበርከትም በላይ በአካባቢው የተቸገሩ ነዋሪዎችን መርዳት እንድንችል ስፖርቱ ትልቅ ሀይል ይሆነናል ይላሉ።
አራት አመታትን ያስቆጠረው የጤና ስፖርት ማህበራቸው ሲጀመር ትንሽ ሆኖ ጊዜያት በረዘሙ ቁጥር ደግሞ አቅሙን እያጠናከረ የአባላት ቁጥሩን እየጨመረ መጥቷል። አሁን ከ90 በላይ አባላትን ይዞ ይንቀሳቀሳል። ለረጅም ዘመናት የአካባቢው ተወላጆችን ጨምሮ በሜዳው ፍቅር ተይዘው ኳስን ለማንከባለል ከአጎራባች ሰፈሮች የሚመጡ ልጆችን ያለልዩነት ሲቀበል የነበረውን ሜዳ ባላቸው አቅም ለማስተካከል ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።
የማህበሩ ሰብሳቢ ዳዊት ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ባደረገው ቆይታ( እጁን ወደ ሜዳው እየጠቆመ) «ይህቺ ሜዳ ለብዙ ሰዎች ባለውለታ ነች» በማለት የቤሌር ሜዳን ታሪካዊ ባለውለታነት ይናገራል። በንግግሩ ለመረዳት የሞከረ ሰው «ታዲያ ውለታ ለሰራችልን ሜዳ ብንሰባሰብላት እና የቀድሞውን ስም እና ዝና ለመመለስ ብንሞክር ምን ይገርማል ሜዳዋ እኮ ሳር ብቻ ሳይሆን ሰውም አብቅላለች» የሚል ድምፀት የተደበቀ ይመስላል። ለመሆኑ ይህቺ ሜዳ እነማንን አፍርታ ይሆን? መልሱ ዳዊት እና ጓደኞቹ ጋር አለ።
አሰልጣኝ ንጉሴ ገብሬ
አስረኛው የአፍሪካ ዋንጫና በ1974 በሊቢያ በተዘጋጀው 13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ኢትዮጵያ እንድትሳተፍ ያስቻሉ ተጠቃሽ ተጫዋቾችን አገራችን አፍርታለች። ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ውለታ ከሰሩት ተጫዋቾች መካከልም መንግስቱ ወርቁ፣ ይድነቃቸው ተሰማ፣ ንጉሴ ገብሬ በቀዳሚነት የሚጠሩ ናቸው። በእነዚህ ሁለት የመጨረሻዎቹ የኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ከፍተኛ ሚና ከነበራቸው ውስጥ አንዱ የሆነው የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋችና በአሁን ሰአት በፕሮጀክት አሰልጣኝነት እየሠራ የሚገኘው ንጉሴ ገብሬ በታሪካዊቷ የቤሌር ሜዳ ላይ ኳስን ካንከባለሉት ውስጥ የሚጠቀስ ነው።
በ1948ዓ.ም የተወለደው ንጉሴ ገብሬ በአዲስ አበባ ቀበና አካባቢ አድጓል። ለንጉሴ ስኬት ቤሌር ትልቅ ትርጉም ነበራት። እርሱም «በልጅነቴ እንደ ማንኛውም ታዳጊ ሰፈር ውስጥ እግር ኳስ እጫወት ነበር፡፡ በትምህርት ቤት ቆይታዬም ኳስ ተጫውቻለሁ» በማለት ይናገራል። ታዲያ የልጅነት የእግር ኳስ ጨዋታው የሚጀምረው በዚችሁ ሜዳ ላይ ነበር። ንጉሴ ለዋናው ብሔራዊ ቡድን ከ1967 እስከ1983 ለ16 ዓመታት ያህል ተጫውቷል።
ባዩ ሙሉ
ሌላኛው በቤሌር ሜዳ ተጫውተው ለስኬት ከበቁ ታዋቂ እግር ኳስ ተጫዋቾች ውስጥ ባዩ ሙሉ ተጠቃሽ ነው። በኢትዮጰያ እግር ኳስ አፍቃሪ ልብ ውስጥ ያለው ባዩ «የቤሌር ሜዳ» እድል ቀንቶት በታዋቂው የቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን ለመጫወት በር ተከፍቶለታል። ባዩ የመጀመሪያውን የምሥራቅ አፍሪካ የታዳጊዎች ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ ይዘው ከመጡ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሲሆን የርሱ ድርሻ ጉልህ ነበር። ከዚህም ሌላ ኬንያ ባዘጋጀችው «የሴካፋ ሻምፒዮና» ላይ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ለመመረጥም በቅቷል።
የምሥራቅ አፍሪካ ውድድር ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአገር ውጪ በሩዋንዳ ዋንጫ ስታነሳ በፍፃሜው ጨዋታ ላይ የማሸነፊያዎቹን ሁለት ግቦች አስቆጥሯል። ባዩ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለት ዓመት በዋናው ክለብ ተሰልፎ ተጫውቷል። የእግር ኳስ ህይወቱ ከማብቃቱም በፊት በቤልጂየም አገር ለረጅም ጊዜ ተጫውቷል። የቀበናዋ ቤሌር ሜዳም ካበቀለቻቸው የአገር ባለውለታዎች ተርታ አሰልፋዋለች።
የቀድሞው ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ እና በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በአሁኑ ሰአት ተሳትፎ የሚያደርገውን መቀሌ ከተማ በማሰልጠን ላይ የሚገኘው ዮሀንስ ሳህሌ በዚህች ታሪካዊ ሜዳ ላይ እግራቸውን አሟሽተዋል። ጌቱ ተሾመ (ድክሬ)፣ ፓውሎስ ማንጎ የመሳሰሉቱ በትንሿ ሜዳ ላይ ኳስን ሲያንሸራሽሩ ነበር። የወደፊት እንጀራቸውንም የወሰነችው ይህችው ሜዳ ነበረች። በቅርብ ጊዜም ይህቺ ታሪካዊ ሜዳ እንደ ቀድሞው ባይሆን እንኳን ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እና ለቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የሚጫወተውን ናትናኤል ዘለቀን አፍርታለች።
ታሪክ ለማስቀጠል
የቤሌር ልጆች«የአስራ አምስት ሜዳና አካባቢው የጤና እግር ኳስ ማህበር የአካባቢያቸውን የቀድሞውን ስም ለማስቀጠል ለአገሪቷ እግር ኳስ እድገት ጉልህ ሚና የሚኖራቸው ታዳጊዎችን ለማፍራት ቆርጠን ተነስተናል» ይላሉ። ሜዳውን ደረጃውን በጠበቀ መንገድ አዘጋጅተው ለሚተኩ ህፃናት ለማበርከት ፍላጎት አላቸው። የአካባቢያቸው ወረዳ ስፖርት ፅህፈት ቤትም በጉዳዩ ላይ ፈቃደኛ ሆኖ ሜዳውን እንዲጠቀሙበት አድርገዋል። ነገር ግን የአራዳ ክፍለ ከተማ ትብብር አነስተኛ እንደሆነ ነው የማህበሩ አባላት የሚናገሩት።
ለሶስት አመታት ልክ እንደሌሎቹ የእግር ኳስ ጤና ማህበራት ሜዳውን በውሰት እንዲሰጧቸው ጥያቄ ቢያቀርቡም በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን ድረስ ሊተባበሯቸው አልቻሉም። አንዴ «በስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶች ሊሰራ ነው» ሌላ ጊዜ ደግሞ «መንግስት እራሱ በጀት ይዞ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ሊገነባው ነው» የሚሉ ምክንያቶች ማህበሩ አቅዶ ሊያከናውነው ያሰበውን ሰፊ ስራ እንዳያከናውን እንቅፋት እንደሆነባቸው ይናገራሉ።
አቶ ሽመልስ ተስፋዬ በቀበና መድሀኒአለም አካባቢ ነው ተወልዶ ያደገው። እግር ኳስን እንደ ሙያ አድርጎ ባይዘውም ለረጅም ጊዜያት ተጫውቷል። ከኳስ ጋር ያስተዋወቀው ይህ ሜዳ ነው። ከጊዜያት በኋላ ግን ሜዳው የቆሻሻ መጣያ መሆን ጀመረ። በሀላፊነት የሚያስ ተዳድረው አካል ባለመኖሩም ለአመታት በዚያ ስፍራ ኳስን ማንከባለል ከሚሰጠው ጥቅም ይልቅ ይዞት የሚመጣው የጤና መዘዝ ከባድ ሆነ። እሁድ እሁድ ጤናውን ለመጠበቅ እግር ኳስን የሚያዘወትረው አቶ ሽመልስም ከአካባቢው እርቆ በካሳንቺስ ሰፈር «መብርቅ» በሚባል የጤና ቡድኑ ውስጥ ተካቶ መጫወት ጀመረ። ሆኖም ግን ሁሌም አንድ የሚቆጨው ነገር ነበር። እርሱ በኖረበት ሰፈር ለብዙሀኑ የእግር ኳስ ህይወት በር የከፈተው ሜዳ እያለ ካሳንቺስ ድረስ እየሄደ መጫወቱ ያሳዝነው ነበር።
ሽመልስ ላይ ቁጭት የተፈጠረበት በሜዳው ላይ አለመጫወቱ ብቻ ሳይሆን፤ አሁን ላይ ያሉት ወጣቶች የቀድሞዎቹን አንጋፋ ተጫዋቾች ፈለግ ተከትለው ውጤታማ የእግር ኳስ ህይወት እንዳይመሩ እና ለአገሪቷ የኳስ እድገት አበርክቶ እንዳይኖራቸው እንቅፋት ስለሆነም ጭምር ነው። ለአንድ ዓመት ያክል በካሳንችስ የመብረቅ የጤና እግር ኳስ ቡድን ውስጥ የተጫወተው ሽመልስ በተፈጠረበት ቁጭት ምክንያት ከቡድኑ መልቀቂያውን ወስዶ በአካባቢው ተመሳሳይ ቡድን ለመመስረት አሰበ። ከአብሮ አደጎቹ ጋር ተመካክሮም አሁን ያለውን ማህበር እውን አደረጉት። ከምንም ነገር በላይ ለእነ ሽመልስ እግር ኳስ እየተጫወቱ የራሳቸውን ጤና መጠበቅ ብቻ ሳይሆን አላማቸው፤ ቀድሞ «የቤሌር ሜዳ» ወጣት ተጫዋቾችን በማፍራት የሚታወቅበትን ስም በድጋሚ መመለስም ጭምር መሆኑን ይናገራል።
«የዚህ ሜዳ በአካባቢያችን መኖር ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው» የሚለው ሽመልስ በዋናነት ሜዳው ለጤና ማህበሩ ከሚሰጠው ጠቀሜታ ይልቅ ታዳጊዎች በማፍራት እና በአገሪቷ እግር ኳስ ላይ ለውጥ ማምጣት ይችላል በማለት ይናገራል። በመሆኑን ማዘውተሪያ ስፍራውን ሁሉም የአካባቢው ህብረተሰብ እና መንግስት ትኩረት ሰጥቶት ሊጠብቀው ይገባል የሚል መልእክት አለው።
ሚኪያስ አምባቸው ሌላኛው የስፖርት ማህበሩ አባል እና ምክትል ሊቀመንበር ነው። በቤሌር ሜዳ ላይ ከልጅነቱ ጀምሮ ከአብሮ አደጎቹ ጋር ይጫወት ነበር። እርሱ እግር ኳስ ከጨዋታም በላይ ነው ይላል። በአካባቢው ላይ የሚኖሩት ወጣቶች ብሎም ጎልማሳዎችን በአንድ ጥላ ስር በማሰባሰብ ማህበራዊ ህይወታቸው እንዲጠናከር የሚጫወተው ሚና ይህነው ተብሎ የሚገለፅ አይደለም ይላል።
«ማህበሩ ከተመሰረተ አንስቶ ባለን አቅም የተቸገረን እና የታመመን እንጠይቃለን» የሚለው ሚኪያስ ይህን ማድረግ የቻልነው ይህ ታሪካዊ ሜዳ አስካሁንም ድረሰ በዚህ ስፍራ በመኖሩ ነው ይላል። ታዋቂ ተጫዋቾችን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ከማበርከት ባለፈ ሜዳው ማህበራዊ ህይወትን በማጠናከር ያለው ፋይዳ ሊታወቅ ይገባል የሚል መልእክት አለው። በዚህ የተነሳ ማዘውተሪያ ስፍራውን የመጠበቅ እና ወደ ተሻለ ደረጃ የማሳደግ ሀላፊነቱ የሁሉም መሆን እንዳለበት ይናገራል።
የአስራ አምስት ሜዳና አካባቢው የጤና እግር ኳስ ማህበር በየወሩ አስፈላጊ ለሆኑ ጉዳዮች እንዲውል መዋጮ ያደርጋሉ። ድጋፍ አድራጊ አካላትን በማስተባበር ሜዳውን ለማሻሻል ይጥራሉ። በሳምንት ሶስት ቀን የልምምድ መርሀ ግብር ሲኖራቸው እሁድ እሁድ ደግሞ ከሌሎች ቡድኖች ጋር የአቋም መለኪያ ውድድር ያደርጋሉ። በቤሌር ሜዳ የማህበሩ አባላት ብቻ አይደለም ጨዋታ የሚያደርጉት። በፕሮጀክት ታቅፈው የሚሰሩ ታዳጊ ህፃናትም አሉ። ትርፍ ጊዜያቸውን ኳስ በመጫወት ማሳለፍ የሚፈልጉ የአካባቢው ነዋሪዎችም በዚሁ ሜዳ ላይ እንደየ ፈርጃቸው ይሳተፋሉ። ጨዋታውን ማየት የሚፈልጉ ሰዎችም በሜዳዋ ዙሪያ መመልከት እየተለመደ ነው። ለዘመናት ሳትሰስት እራሷን የሰጠችው ሜዳም ትንሽ ከትልቅ ሳትል ሁሉንም ተቀብላ ታስተናግዳለች። እርሷ የባረከችው ደግሞ እንደ ንጉሴ ገብሬ እና ሌሎች አንጋፋ ተጫዋቾች ተባርኮ የህይወት መስመሩን ይዟል።
እግር ኳስን ለበጎ ተግባር
የ15 ሜዳና አካባቢው ጤና ስፖርት ማህበር በጎ ስራን እየሰራ ነው ሲሉ በምሳሌነት የሚጠቅሱት ነገር አላቸው። እግር ኳስን ከጨዋታ በላይ ለመልካም ነገር ትውላለች ሲሉም ከዚህ መነሻነት ነው። ማህበሩ የተመሰረተው ከስፖርታዊ ውድድሮች ጎን ለጎን የተቸገሩና አቅም የሌላቸውን ለመርዳት በመሆኑም በአንድ ወቅት የጤና እክል ያጋጠመው እዮብ ብርሀኑ(አቢቲ) ለሚባለው አብሮ አደጋቸው ድጋፍ አድርገዋል።
እዮብ ብርሀኑ በቅፅል ስሙ (አቢቲ) ባጋጠመው ህመም ምክንያት ወደ ውጭ ሄዶ ለመታከም የተጠየቀው ገንዘብ ከአቅም በላይ በመሆኑ የጤና ስፖርት ማህበሩ ከጎኑ በመቆም በ12 የጤና ቡድኖች መካከል ውድድር በማድረግ ለህክምና የሚረዳውን ገንዘብ አሰባስበዋል። እነ ባዩ ሙሉ፣ ደብሮም ሀጎስና ሌሎች የቀድሞ ታዋቂ ተጫዋቾች ተሳትፈውበታል።
በወቅቱ በተደረገው ጨዋታ በባዩ ሙሉ አምበልነት እየተመራ የ15 ሜዳና አካባቢው የጤና ቡድን 2ለ1 በማሸነፍ ዋንጫ አግኝቶ ነበር። ጨዋታው ከማሸነፍ እና ከመሸነፍ በላይም ሰብአዊነትን እና መደጋገፍን ለሁሉም የስፖርት ቤተሰብ ያሳየ ነበር። በርካታ ተመልካች በታደመበት ጨዋታ በአካባቢው ያደጉት የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌና እንዲሁም ንጉሴ ገብሬ በእንግድነት ተገኝተው ነበር። ሜዳዋም የቀድሞ ልጆቿ ለበጎ ተግባር ሲሰባሰቡላት እንዲሁም አዲስ ተስፋ ያላቸው ታዳጊዎች በብሩህ ተስፋ ሲሰንቁ ስትመለከት በደስታ ሳትፈነድቅ አትቀርም።
አሰልጣኙ ምን ይላል?
ኤሊያስ ኢብራሂም ይባላል። በደደቢት እግር ኳስ ቡድን ውስጥ ምክትል አሰልጣኝ ነው። የአስራ አምስት ሜዳና አካባቢው የጤና እግር ኳስ ማህበር በበጎ ፍቃድ ያሰለጥናል። ለሶስት አመታት ያህልም በቤሌር ሜዳ ቡድኑን ሲያሰለጥን ቆይቷል። በእድሜ ከእነርሱ ትንሹ ቢሆንም ባለው የማሰልጠን ክህሎት ሁሉንም አባላቱን አስፈላጊውን ሳይንሳዊ የእግር ኳስ መርህ ያሰራቸዋል። እነርሱም ቢሆኑ በመልካም ስነ ምግባር ከኤሊያስ ጋር ልምምዳቸውን ያደርጋሉ።
እንደ አሰልጣኙ አመለካከት «አካባቢው ላይ ተዳክሞ የነበረውን እግር ኳስ ለማንሳት» የዚህ ማህበር መመስረት ትልቅ ፋይዳ ነበረው። ጎልማሶች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በዚህ ሜዳ ላይ ማድረጋቸው በቀዳሚነት የራሳቸውን ጤና እንዲጠብቁ እረድቷቸዋል። ከዚህ አንፃር ማህበራቸው ግቡን እያሳካ ነው። በሌላ መልኩ በመሰረታዊ ሁኔታ ታዳጊዎች ሞራል ሰንቀው በተሻለ ተስፋ እና ምቹ በሆነ ሜዳ እንዲጫወቱ ስብስቡ የበኩሉን አስተዋፆ አድርጓል።
ኤሊያስ ለቡድኑ አባላት በሳምንት ሶስት ጊዜ ስልጠና ይሰጣል። በኮሚቴዎቹም ላይ በመሳተፍ ያለውን ሙያ ሳይሰስት ያካፍላል። ምክንያቱም ተጫውቶ ያደገባት ሜዳ ትወቅሰዋለችና። ከዚህም ሌላ ታሪካዊው ስም ወደ ቀድሞው ስፍራ ተመልሶ አሁንም ታዋቂ እና አንጋፋ ተጫዋቾች ከአካባቢው እንዲወጡ ይፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ሙያዊ እገዛ ማድረጉ የውዴታ ግዴታው ይሆናል።
ኤሊያስ የእግር ኳስን ክህሎት ያዳበረው እና ፍቅሩን ያገኘው አሁን በአሰልጣኝነት ከሚመራው የጤና ቡድን አባላቶች ነው። በሰፈር ውስጥ እነርሱን እየተመለከተ ነው ያደገው። ከዚያ ባለፈ ግን አሁን ስብስቡን በመልካም ስነምግባር የታነፀ እግር ኳስን ለጤናና ለማህበራዊ ሀላፊነት ለመወጣት የሚጫወት አድርጎ የማሰልጠን ሀላፊነቱን ተቀብሏል። የእግር ኳስ እና የአሰልጣኝነት ክህሎቱ ደግሞ የጤና ማህበር ቁንጮ አሰልጣኝ ሆኖ እንዲመረጥ አድርጎታል።
አሰልጣኙ ቡድኑ ከጤና አኳያ ምን አይነት ሳይንሳዊ የእግር ኳስ ልምምድ ማድረግ እንዳለበት ይወስናል። እነርሱም ይህንን ተከትለው ልምምዳቸውን ያደርጋሉ። በዚህ ረገድ አሰልጣኝ ኤሊያስ ስኬታማ እንደሆነ ይናገራል። «በሁለት ቡድን የተከፈሉት የማህበሩ አባላት እንዲያውም ክለቦች ከሚሰሩት ልምምድ በላይ ነው የሚሰሩት» በማለት ያላቸውን ተነሳሽነት ይመሰክራል። እርሱም አካላዊ ጤንነታቸው የተስተካከለ እንዲሆን ከማድረጉም ባለፈ የቡድን እና የአጋርነት መንፈስ እንዲኖራቸው እገዛ አድርጎላቸዋል።
ኤሊያስ አብዛኛውን የልጅነት ጊዜውን በቤሌር ሜዳ እግር ኳስን በመጫወት እንዳሳለፈ ይናገራል። ወደኋላ መለስ ብሎ የልጅነት ጊዜውን ሲያስታውስ የማዘውተሪያ ስፍራው ለአካባቢው ወጣቶች በቃላት የማይገለፅ ትልቅ አስተዋፆ ማበርከቱን ነው በቅድሚያ በአእምሮው ላይ የሚከሰትለት። ከዚያም በዘለለ «አሁን ላለሁበት ደረጃ ሜዳው የህይወቴ መሰረት ነው» በማለት እርሱ እና እግር ኳስ ሜዳው ያላቸውን ቁርኝት ይገልፃል።
ለኤሊያስ ቤሌር ከእግር ኳስ ሜዳም ባለፈ እራሱ እግር ኳስ ምን እንደሆነ ያስተዋወቀው ነው። ስለዚህ ሁሌም ለዚህ ስፍራ የተለየ ክብር አለው። «ከመሰረታዊ የእግር ኳስ የታዳጊዎች ፕሮጀክት አንስቶ ክለብ እንድመሰርት የዚህ ታሪካዊ የማዘውተሪያ ስፍራ መኖር ጠቅሞኛል» በማለት ይገልፃል። የጤና ስፖርት ማህበሩ እና እርሱ በግል የጀመረው የታዳጊዎች ፕሮጀክት ቤሌር ሜዳ እንዲሁ የቆሻሻ መጣያ ሜዳ ሆኖ እንዳይቀር ትልቅ ትግል አድርገዋል። ታሪካዊነቱን ጠብቆ እንዲቆይ ከማድረግም በዘለለ ታዳጊዎች በዚህ ስፍራ ውጤታማ ስፖርት ተጫዋች ሆነው እንዲያድጉ ይህን ማዘውተሪያ ስፍራ ወደ ተሻለ ደረጃ ማሳደጉ ተገቢ በመሆኑም ጭምር ነው።
ኤሊያስ በእርሱ እድሜ በዚህ ስፍራ ከልጅነታቸው ጀምሮ እግር ኳስን በመጫወት ትልቅ ስፍራ ደርሰዋል። ለአገራቸውም ስፖርት አበርክቷቸው ሰፊ ነው። ያላቸውን እነ ጌቱ ተሾመ፣ ባዩ ሙሉ፣ ደብሮም ሀጎስ፣ መስፍን ደምሴ «ድክሬ» እና ቻይና አድማሱ የመሳሰሉ ሰዎች በድጋሚ በዚህኛው ትውልድ፤ በዚህች ታሪካዊ ሜዳ ላይ ማፍራት ይኖርብናል ይላል። ለዚያም ነው በርካታ ታዳጊዎችን በፕሮጀክት አቅፎ በማሰልጠን ላይ የሚገኘው። ለልጆቹ መልካም ስነምግባር መቀረፅ ደግሞ «የጤና ቡድኑን» ራእይ እንዲከተሉ መንገዱን በመክፈት ላይ ነው የሚገኘው።
ኤሊያስ «ራእይ ታዳጊዎች የእግር ኳስ ፕሮጀክትን» ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ አቋቁሞ በዚሁ ቤሌር ሜዳ ላይ እያሰለጠነ ቆይቷል። ሶስት ቡድኖችንም በተለያየ ዓመት በማሰልጠን ለተለያዩ የእግር ኳስ ክለቦች እንዲመለመሉ አስችሏል። ይህ ሜዳ ባይኖር አሁንም እነዚህን ወጣቶች ማብቃት አይቻልም ነበር የሚል አመለካከት አለው። የረጅም ዓመት እቅዶችን በማውጣትም እየሰራ ነው።
ኤሊያስ የሚመራው የታዳጊዎች ፕሮጀክት እና «የአስራ አምስት ሜዳና አካባቢው የጤና እግር ኳስ ማህበር» በርካታ እንቅፋቶች እንደሚያጋጥማቸው ያነሳሉ። ሆኖም የተነሱበትን አላማ ለማሳካት ካላቸው ፍላጎት እና ጉጉት አንፃር ለረጀም ዓመታት መፍትሄ ሲፈልጉላቸው እና ጎንበስ ብለው ሲያልፏቸው ነበር። ነገር ግን ይህን ችግር ይፈቱልናል ያሏቸው አካላት ድጋፍ ቢያደርጉላቸው መንገዳቸው ቀና ስለሚሆን «ተባበሩን» የሚል ጥሪ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ያስተላልፋሉ። በዚህም ታሪካዊውን ሜዳ ዘመናዊ ለማድረግ ብሎም የእግር ኳስ ማህበሩን እና ፕሮጀክቱን በገንዘብ አቅም ለመደገፍ የሚፈልጉ ባለሀብቶች እንዲሁም የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው ይላሉ። ምክንያቱም «ሜዳው ሳር ብቻ ሳይሆን ሰውም ያበቅላልና»

ዳግም ከበደ

Published in ስፖርት

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።