Items filtered by date: Monday, 05 February 2018

በረጅም ርቀት ሩጫዎች ብዙ አገራት በማይታ ወቁበት ዘመን የምስራቅ አፍሪካ አገራት ተጽዕኖ አሳዳሪዎች ነበሩ። በተለይ ኢትዮጵያና ኬንያን የመሳሰሉት አገራት አትሌቶች በርቀቶቹ ገንነው ከመታወቃቸው ባሻገር በሚሳተፉባቸው ውድድ ሮችም የበላይነቱን በመያዝ ነበር የሚያጠናቅ ቁት። ምዕራባወያኑ አገራትም ለዓመታት ተግተው በመስራታቸው በርቀቶቹ ተፎካካሪነ ታቸውን በማስመስከር ላይ ይገኛሉ። በአንጻሩ ኢትዮጵያን መሰል አገራት ከጊዜው እኩል መራመድ ባለመቻ ላቸው በተለመደው ርቀት ያላቸው ተፎካካሪነት በመቀነስ ላይ ይገኛል። በመሆኑም አዲስ መንገድ መቀየስና ሌሎች ተሞክሮዎችን መቅሰም አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በተለይ ለአጭር ርቀትና ለሜዳ ተግባራት ስፖርቶች ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል። አገሪቷ ወደፊት ውጤታማ ለመሆን ባቀደችባቸው በእነዚህ ስፖርቶች ምን ዓይነት ተግባራት በመከና ወን ላይ ይገኛሉ? የሚለውን አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጠይቋል። ለውጤታማነቱ የመጀመሪያውን ሚና ከሚጫወተው ስልጠና እስከ ውድድር ያለውን ሂደትም የፌዴሬሽኑ ባለሙያዎች ገለጻ አድርገዋል።
ቅድመ ሁኔታ
ፌዴሬሽኑ ያለፈው ዓመት ባለሙያዎቹን በመላ አገሪቷ በማሰማራት አትሌቲክሱ በምን ዓይነት መንገድ እየተዘወተረ ነው በሚለው ላይ ምልከታ አድርጓል። በዚህም የተሰሩ ሥራዎችንና ክፍተቶችን የመለየት ሥራ መከናወኑን በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስልጠናና የጥናትና ምርምር የሥራ ሂደት መሪ አቶ ሳሙኤል ብርሃኑ ይገልጻሉ። ይህንኑም ለክልሎች በማሳወቅና ከብሄራዊው ፌዴሬሽን ምን ይጠበቃል የሚለውን በመለየት አቅጣጫ የመቀየስ ሥራ ተከናውኗል።
የተወሰዱ ርምጃዎች
የፌዴሬሽኑ ባለሙያዎች በተያዘው ዓመትም ወደ ክልሎች በመጓዝ ከምልመላ ጀምሮ የሚሰጠው ስልጠና እንዲሁም የውድድር ሥርዓታቸው ምን ይመስላል በሚለው ላይ ሙያዊ ድጋፎችን ለማከናወን ሙከራ ተደርጓል። በዚህ እንቅስቃሴ ከሚካተቱት መካከል የአጭር ርቀትና የሜዳ ላይ ተግባራት ቀዳሚዎቹ ሲሆኑ፤ የባለሙያዎቹ ቡድንም በተለይ ትኩረት የሰጠው ለእነዚህ ስፖርቶች እንደነበር የሥራ ሂደት መሪው ይገልጻሉ። በዋነኛነት ለስፖርቱ መዳከም በምክንያትነት የሚነሳውም የስፖርተኞች የአመላመል ስርዓት መሆኑን ለመመልከት ተችሏል፡፡ ስፖርተኞችን ማፍራት የሚችሉ ቦታዎችንም በመምረጥ ላይ ውስንነቶች ነበሩ።ስልጠናው የሚሰጥባቸው ቦታዎች ከባህር ጠለል በላይ የሚገኙበትን በመመልከት እንዲሁም የአኗኗር ሁኔታቸውን በማጥናት ለየትኛው የስፖርት ዓይነት ምቹ ነው የሚለውንም ለይተዋል። በዚህም የአየር ሁኔታው፣ የቦታ አቀማመጡ እና የህብረተሰቡ አኗኗር ለስፖርቱ ምቹ መሆናቸው በባለሙያዎች የተረጋገጡና ከዚህ ቀደም የማሰልጠኛ ተቋማት ያልነበሩባቸውን ቦታዎችም ለመለየት ተችሏል። ይህም ብቻ ሳይሆን በፌዴሬሽኑ በተቀመጠው ስታንዳርድ መሰረት አዳዲስ አትሌቶችን የመመ ልመል ሥራዎችም ተሰርተዋል።
በስፖርት ማዘውተሪያና ቁሳቁስ
አገሪቷ ውጤታማ የሆነችበት የረጅም ርቀት ዘርፍ ከግለሰቦች ጥረት ባሻገር የእለት ተእለት አኗኗርም ከፍተኛውን ሚና የሚጫወት ነው። አሰልጣኝና ደረጃውን የጠበቀ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላት ባልተሟሉባቸው ወቅትም አትሌቶች በታደሉት ተፈጥሮ ታግዘው ስመጥር መሆናቸው ይታወቃል። በአንጻሩ የአጭር ርቀት አትሌቲክስና የሜዳ ላይ ተግባራት ከተክለ ቁመና ጀምሮ በስልጠና ሂደት ላይም የስፖርት ቁሳቁስና የአመጋገብ ሥርዓት ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው።
በተለይ በእነዚህ ስፖርቶች አስፈላጊ የሆኑት ግብዓቶች በቀላሉ የማይገኙና ውድ መሆናቸው ይታወቃል። በክለቦችም ሆነ በስፖርት ማሰልጠኛ ተቋማት የሚሰለጥኑ አትሌቶች ቁሳቁሶቹን የማግኘት ዕድላቸው አናሳ መሆኑም አገሪቷ በስፖርቱ ውጤታማ ላለመሆኗ እንደ አንድ ምክንያት ይነሳል። አብዛኛውን ጊዜም ሰልጣኞች በአካባቢያቸው በሚያገኟቸው ቁሳቁሶች ታግዘው አስመስለው በሚሰሯቸው
የስልጠና መሳሪያዎች ነው የሚሰለጥኑት። ይህም ደረጃውን ባልጠበቀ ቁሳቁስና የማዘውተሪያ ሥፍራዎች ሰልጥኖ ያላለፈን ሰልጣኝ በውድድሮች ላይ ውጤት ያመጣል ብሎ መጠበቅ የማያስችል ያደርገዋል።
ከጉብኝቱ ጋር ተያይዞም ፌዴሬሽኑ በማዘ ውተሪያ ሥፍራዎች እና በስፖርት ቁሳቁስ ላይ ትኩረት ያደረገበት እንደነበር የሥራ ሂደት መሪው አቶ ሳሙኤል ያስታውሳል። ክልሎችም ከዚህ ቀደም በቁሳቁስ አቅርቦት ላይ አበረታች የሚባል ሥራ አለመስራታቸውም ተስተውሏል። ይህንኑ ችግር ለመፍታትም ፌዴሬሽኑ በአነስተኛ ዋጋ ከሚያቀርቡ ከአገር ውስጥ አምራች ድርጅቶች ጋር በመነጋገር ላይ መሆኑም ተጠቁሟል። በተለይ እንደየ ሰልጣኙ ዕድሜ፣ ለውድድርና ለስልጠና በምን ያህል መስፈርት መዘጋጀት ይገባል? እንዲሁም ለየክልሎቹ ምን ያህል አቅርቦት ያስፈልጋል? በሚለው ላይም ፌዴሬሽኑ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።
የስልጠና ባለሙያዎች
የረጅም ርቀት አትሌቲክስ ረጅም ዓመታተን እንደማስቆጠሩ በልምድ ታግዘው የሚያሰለጥኑ በርካታ አሰልጣኞች መፈጠራቸው ይታወቃል። የአጭር ርቀትና የሜዳ ላይ ተግባራት ደግሞ በተለይ በሳይንሳዊ ዘዴ የተቃኙ መሆን ይገባቸዋል። ከአትሌቶች አመላመል ጀምሮ በስልጠና ሂደት ላይም በርካታ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን መገንዘብ አስፈላጊ ይሆናል።
በአገሪቷ ያሉት አሰልጣኞች ቁጥር ከስልጠናውና ከሰልጣኞቹ ጋር የሚመጣጠን አለመሆኑም በባለሙያዎቹ ተረጋግጧል። በአህጉርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ ተሳትፈው ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉ አትሌቶችን ለማፍራት በሚያስችል እውቀት የዳበሩ እና ሙሉ ሊባሉ የሚችሉ አሰልጣኞች አገሪቷ በምትፈልገው መጠን የሉም። ይህንኑ ችግር ለመቅረፍም ፌዴሬሽኑ ያቀደው አሰልጣኞችን ከውጭ አገራት ለማስመጣት ነው። ልምድ ያላቸውን አሰልጣኞች ለማስመጣት በሙከራ ላይ ሲሆን፤ አሰልጣኞቹ ለኢትዮጵያውያን አሰልጣኞች ልምድና ተሞክሮዎችን እንደሚያ ካፍሉም የሚጠበቅ ነው።
ውድድር
በየትኛውም ደረጃ ስልጠናው ምን ይመስላል የሚለውን ለመዳኘት በውድድር መፈተሽ አስፈላጊ ይሆናል። በዘርፉ የሚዘጋጁ ውድድሮች ምን ይመስላሉ የሚለውንም በፌዴሬሽኑ የተሳትፎና ውድድር ንኡስ የሥራ ሂደት መሪ አቶ አስፋው ዳኜ ያብራራሉ። ትናንት የተጠናቀቀውን የኢትዮጵያ ክለቦች የአጭር፣ የመካከለኛ፣ የእርምጃ እና የሜዳ ተግባራት ሻምፒዮና ጨምሮ በዘርፉ በሚካሄዱ ውድድሮች የሚመዘገበው ውጤት፤ ከሌላው ዓለም አንጻር በርካታ ቀሪ ነገሮች መኖራቸውን የሚጠቁም ነው። በመሆኑም የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ስፖርቱ በምን ዓይነት መንገድ ሊያድግ ይችላል በሚለው ላይ እየሰራ እንደሚገኝ ይገልጻል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውድድሮች ላይ ተሳታፊ ከሚሆኑት አትሌቶች በርካታዎቹ አዳዲስ መሆናቸውን አቶ አስፋው ይጠቅሳሉ። በተተኪ አትሌቶች ይቀርብ የነበረው ትችት ምላሽ ሊያገኝ በሚችልበት ሁኔታ ላይ የሚገኝና እንደየርቀቱም ተመጋጋቢ የሆኑ በርካታ አትሌቶች መኖራቸው ተስተውሏል። አትሌቶቹ በስልጠና ሂደት የስፖርት ቁሳቁሶችን በሚፈለገው ልክ አለማግኘታቸው በውድድር ላይ ተጽዕኖ እንዳላሳደረባቸውም ነው የታየው።
ስፖርቱን ለማሳደግ ውድድሮቹን ማበራከትም ሌላኛው መንገድ መሆኑ እውን ነው። በመሆኑም በየዓመቱ ከሚዘጋጀው ሻምፒዮና ባሻገር ሌሎች ውድድሮችን ማዘጋጀት የግድ ይሆናል። ፌዴሬሽኑ በዓመቱ ካቀዳቸው ውድድሮች መካከል በእነዚህ ስፖርቶች ውድድር ማዘጋጀት አንዱ ሲሆን፤ ይህም አትሌቶቹ በአገር ውስጥ በርካታ የውድድር መድረክ አግኝተው ራሳቸውን እንዲፈትሹ ያደርጋቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ተፎካካሪነቱን ለመጨመርና ስፖርቱንም ለማበረታታት በውድድሮቹ አሸናፊ ለሚሆኑ አትሌቶች ከዚህ ቀደም ባልታየ መልኩ ዳጎስ ያለ የገንዘብ ሽልማትም በፌዴሬሽኑ እየተዘጋጀ መሆኑን አቶ አስፋው ያስረዳሉ።
መልዕክት
ፌዴሬሽኑ ስልጠናውን ሳይንሳዊ በሆነና ዓለም በዚህ ወቅት በሚገኝበት መንገድ ለመምራት በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ የፌዴሬሽኑ ባለሙያዎች ይጠቅሳሉ። ከዚህ ቀደም የአገሪቷን ስም ያስጠሩ አትሌቶች እዚያ ቦታ ሊገኙ የቻሉት በግል ጥረታቸው ነው። በዚህ ወቅት ደግሞ የግል ጥረት እንዳለ ሆኖ ድጋፍ አስፈላጊ በመሆኑ ከታች ጀምሮ ስልጠና መስጠት የግድ ይላል። ፌዴሬሽኑም በዚህ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፤ ነገር ግን በአንድ ጀምበር የሚስተካከል ነገር ባለመሆኑ የስፖርት ቤተሰቡ በትዕግስት ይጠብቀን በማለት መልዕክ ታቸውን ያስተላልፋሉ።

ብርሃን ፈይሳ

Published in ስፖርት
Monday, 05 February 2018 17:04

“እማማ ንቅሴ”

ልጅ እያለሁ የአያቴን ገጽ ትኩር ብዬ ስመለከት የሚያስገርመኝ በግንባሯ፣ በአገጯና በእጇ ላይ ያሉት ምልክቶች ነበሩ። ምልክቶቹ በትክክል ምን እንደሆኑ ባይለዩም ጥቁር ቀለም ያላቸው በመሆናቸው ደበዘዙ እንጂ ከፊቷ ላይ ጨርሶ አልጠፋም ነበር። በእርጅና የተ ጨማደደውን ለስላሳ ቆዳዋን እያቃናሁ ስመለከት ግን ግንባሯና እጇ ላይ ያሉት ምልክቶች የመስ ቀል አገጯ አካባቢ ደግሞ ሌላ ዓይነት መሆናቸውን ለየሁ።
ስለንቅሳቷ በጠየቅኳት ጊዜም በዘመኑ ልጃገረዶች ለውበታቸው ማድመቂያ በሚል እንደሚ ነቀሱት ትነግረኛለች። ንቅሳት በእነርሱ ዘመን የውበት መገለጫ ቢሆንም በእኛ ዘመን ግን የማይወደድና የኋላ ቀርነት ምልክት እንደሆነም ነበር የምታጫውተኝ። አያቴ ይህንን ካጫወተችኝ ዓመታት አልፈዋል፤ ንቅሳትም በድጋሚ የውበት መገለጫ ሆኖ እና ራሱን አዘምኖ መጥቷል። አያቴ «የኋላ ቀርነት ምልክት» ያለችኝን ንቅሳት የአሜሪካዋ ነዋሪ ቢሰሙት ግን አይዋጥላቸውም። ምክንያቱም እኚህ የአያቴ እኩያ የሆኑ ባልቴት «ንቅሳቴ፤ ውበቴ» ብለው ማጌጥ ከጀመሩ የሰነባበቱ ሲሆን፤ በዚሁ ምክንያትም «እማማ ንቅሴ» የሚል ቅጽል አትርፈዋል።
ቻርሎቴ ጉተንበርግ የተባሉት እኚህ የ 69 ዓመት ባልቴት መኖሪያ ቸውን በአሜሪካዋ የፍሎሪዳ ግዛት ያደረጉ ሲሆን፤ በንቅሳታቸው ምክንያትም ስማቸው በዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ሊሰፍር በቅቷል። እማማ ንቅሴን በቅድሚያ ያያቸው ሰው ከራስ ጸጉራቸው እስከ እግር ጥፍራቸው ዥንጉርጉር ቀለም ያለው ወጥ ልብስ የለበሱ ይመ ስላል። ነገር ግን ይህ ልብስ የመሰለውና ከአካላቸው ከ98 ከመቶ በላይ የተሸፈነው በንቅሳት መሆኑን ማረጋገጥ ይችላል።
ባልቴቷ እስከ 50 ዓመታቸው ድረስ አንድም ንቅሳት በሰው ነታቸው ላይ አልነበረም። ከዚያ በኋላ ጀምረውት ግን እአአ በ2015 ከአካላቸው 91 በመቶ ውን በማዳረሳቸው ስማቸው በመዝገቡ ለማስፈር ችለዋል። ይህ አልበቃ ያላቸውና ለንቅሳት ልዩ ፍቅር ያላቸው አዛውንቷ ፊታ ቸውንና አንዳንድ የአካል ክፍሎቻ ቸውን ብቻ በማስቀረት በተጨማሪ ሊያስውቡት (እንደ እርሳቸው አባባል) ችለዋል። የድንቃድንቅ መዝገቡም «የዓለም ቁጥር አንዷ ባለ ንቅሳት ሴት» ሲል በድጋሚ መዝግቧቸዋል።

Published in መዝናኛ
Monday, 05 February 2018 17:03

የኑሮ ማስታወሻ

ኑሮአችን እንደ ዕድሜያችን የራሱ ቀለምና አቋም ይኖረዋል። ሳንወለድ በፊት የነበርንበትን የኑሮ ሁኔታ ባናስታውሰውም ቅሉ መራራም ይሁን ጣፋጭ ልጅነታችን ግን እስከወዲያኛው ከአእምሯችን ጓዳ የሚሻር አይደለም። ያው ኢትዮጵያውያን ስለሆንን ወደድንም ጠላንም ልጅነታችንን «አፈር ፈጭተን፤ ውሃ ተራጭተን» የሚል ርዕስ እንሰጠዋለን እንጂ። ሆነም ቀረ በጊዜው ኑሯችንን በራሳችን የመዘወር አቅሙ ስለሌለን ባጣፈጡልን ልክ እያጣጣምን ባመረሩብን መጠን ደግሞ ተናንቆን እየዋጥን፤ መነሻውን እንጂ መድረሻውን የማናውቀውን ኑሯችንን እናስቀጥላለን።
ፈረንጆቹ ሕይወትን ከ«ቢ» እስከ «ዲ» ርዝመት ያለው ፍቺ ይሰጡታል። በእነርሱ ቋንቋ መሠረት «ቢ»፤ «በርዝ» ወይም ውልደት ሲሆን «ዲ» ደግሞ «ዴዝ» ወይም ሞት ማለታቸው ነው፤ የሕይወታችንን ርዝማኔ ልኬት ደግሞ በ«ሲ» የሚወሰን ይሆናል። «ሲ፤ ቾይዝ» የሚለውን ቃል የሚወክል ሲሆን፤ ይህም ሕይወታችንን በምርጫችን እንደምንመራት ለማስረዳት ነው። ይህ አባባላቸው ግን ለእኛ ኑሮ የሚሆን አይመስለኝም፤ምክንያቱም እኛ ከዕድሜያችን ሩቡን በተቀደደልን ቦይ ስንፈስ የኖርን ሰዎች ነን። በሌላ ሰው እጅ የተበጀ ቦይ ደግሞ በተቀየሰለት አቅጣጫ እንዲጓዝ እንጂ መድረሻው የት ይሆናል የሚለውን የመወሰን ብቃት አይኖረውም።
እናማ አብዛኛዎቻችን በምፈልገውና በሚገባን ቦታ ሳይሆን በሌላ አቅጣጫ ቆመን ራሳችንን እናገኘዋለን። ያም ሆኖ ወጣትነት የራሱን መልክ ይዞ ብቅ ሲል ሕይወት በምትሰጠን ምርጫ ራሳችንን እናስጉዛለን። በዚህ ዕድሜ ያለው የኑሮ መልክ በአብዛኛው የተዥጎረጎረጎረ እና ትንሽ ቁም ነገርን ከብዙ ዋዛ ጋር ያዳቀለ ይሆናል። በዚህ ዘመን ኑሮን በስንፍና እና በግድ የለሽነት መምራት፤ «ሕይወት አጭር ናት፤ አጣጥማት...» የሚልን ብሂል አንሻፎ በመፍታት ወዲያ ወዲህ እያሉ መኖር የተለመደ ነው። በወጣትነትና ወጣቶች ባልተገነዘቡት ኑሮአቸው ላይ ከተቀለዱት ጥቂቱን ለማስታወስ ያህል፡-
«ወጣት የነብር ጣት» ከሚለው በተቃራኒ የቆመን ወጣት «ምነው ሰነፍክ?» ቢሉት
«ሰንፌ ሳይሆን፤ ጉልበቴን እያጠራቀምኩ ነው» ብሎ ለስንፍናው እውቅና ሰጥቷል።
አንድ አባት ደግሞ ለቁም ነገር በበቁ ጥንዶች ሠርግ ላይ ሲጠሩ ሁሌም ለወጣት ልጃቸው ሞራል እንዲሆነው በማሰብ አስከትለውት ይሄዳሉ። ታዲያ በየሠርጉ ወጣቱን የሚያገኙት የአባቱ ወዳጆች ሁሌም «ቀጣዩ አንተ ነህ» ይሉታል፤ እርሱ ግን የሚያስበው ስለ ጎጆ መመስረት ሳይሆን ጥያቄያቸውን እንዴት ማስቆም እንደሚችል ነበር። እናማ የቀየሰው ዘዴ በቀብር ሥነ ሥርዓቶች ላይ እየተገኙ እነርሱ የሚሉትን ቃል በቃል እየደገሙ «ቀጣይ እናንተ ናችሁ» ማለትን ነው። ታዲያ «የወጣትነት ቀለሙ ዋዛ ማብዛቱ» የሚል ተረት አያስተርትም ትላላችሁ።
ዘመናችን የኤሌክትሮኒክስ ነውና በማህበራዊ ድረገጾች ሱስ የተተበተበና ፌስቡክን እንደ አንድ የሕይወት ቅመም ያደረገ ወጣት ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም። እንዲያውም ኑሮውን ከኢንተርኔት መለየት አቅቶት፤ አንተ እንደማትጠ ቀማቸው ስትነግረው «እውነት? ሕይወትን ያለ ኢንተርኔትና ፌስቡክ እንድንኖር የሚያስችል 'ሊንክ' ካለ ላክልኝ» ብሎ ጭራሽ ግራ ያጋባሃል።
እንዲህ እንዲህ እያለ ጊዜው ብርርርርር ብሎ ሲያልፍ ጎልማሳነት ቦታውን ይረከባል። ይሄኔ ታዲያ ምራቅን ዋጥ ማድረግ ስለ ኑሮም ማሰብ ይጀመራል። እመኑኝ በዚህ ዕድሜ ያጋጠመን ሁሉ እያፈሱ መውሰድ እንጂ ላጣራ ብሎ ነገር አይታሰብም፤ ምክንያቱም ጥሩውም ይሁን መጥፎውም ነገር ለነገው ሕይወት ስንቅ መሆኑን ያውቃል። በዚህ ዘመን ኑሮ ወጥ እየሆነ ይሄዳል፤ ቀለሙም እየጠራ። የምታደርጋት ነገር፣ የምትረግጣት እርምጃ እና የምትወስናት ጉዳይ ሁሉ ለነገ ዋጋ እንደምታስከፍልህ ታቃለህና የረጋ አእምሮህን ትጠቀማለህ።
ድሮ በወጣት ሳለህ ጨለማን ትፈራ ከነበረ በጎልማሳነትህ ነገሩ የተገላቢጦሽ ይሆንና መብራትን ትፈራለህ። ምክንያቱም የሚታይህ ወር ደርሶ ለኤሌክትሪክ ፍጆታህ የምትከፍለውን የገንዘብ መጠን ነዋ። የበረረውን የወጣትነትህን ዕድሜ የምታካክሰው በዚህኛውስለሆነ ታታሪነት ህን በእጥፍ ትጨምረዋለህ።
ያው ቀናት ሲቆጠሩ እርጅና መምጣቱ አይቀርም። ይሄ ዕድሜ ቅርጹ የማይታወቅ ቀለምም የሌለው ነው። ወዳጄ ሃሳቤን እንዳብራራ የምትጠብቀኝ ከሆነ አትድከም፤ ምክንያቱም ከላይ ያነበብከውን ሁሉ የምታስበው በዚህኛው ዕድሜህ ነዋ። መቼም ትረዳዋለህ የእርጅና ቀለምና ቅርጽ በትዝታ መኖሩ ነው። 

ብርሃን ፈይሳ

Published in መዝናኛ

አቶ ሰለሞን ሶሬሳ የዱከም ነዋሪ ናቸው፡፡ ቀደም ሲል ለማንበብና መፃፍ እንግዳ ነበሩ፡ የሚያነቡና የሚፅፉ ሰዎችን ከመመልከት ባለፈ ድርሻ አልነበ ራቸውም፡፡ ሌሎች የተማሩ ሰዎች የሚከና ውኗቸውን ተግባራት ለመፈፀም ቢፈልጉም ያለመማራቸው እንቅፋት ሆኖባቸዋል፡፡ ቢሆንም ግን አንድ ቀን የተሻለ ነገር ሊኖር እንደሚችል ተስፋ ያደርጉ ነበር፡፡
የልባቸው ሃሳብ ሞልቶ ነገሮች ተሳኩ፡፡ እነሆ ከሁለት ዓመት በፊት በዱከም ከተማ ከቀለም ጋር አንድ ብለው ተዋወቁ፡፡ በወጣትነት ዘመናቸው ያላገኙት ዕድል በእርጅና ዘመናቸው ከበራቸው ላይ ሆኖ አንኳኳ፡፡ ትምህርት ለሁሉም በሚለው መርህ መሠረትም የጎልማሶች ተግባር ተኮር ትምህርትን ለመቅሰም ሃሳባቸውን አጠነከሩ፡፡ በእርጅና ዘመናቸው ደብተራቸውን ሸክፈው ወደ ትምህርት ቤት መመላለስ ጀመሩ፡፡ በቃ የ‹‹አስኳላ›› ተማሪ ሆኑ፡፡ በዚህም ቀድሞ ይናፍቁት የነበረውን ሕይወት አገኙት፡፡
አቶ ሰለሞን ዛሬ ማንበብ እና መፃፍ ችለዋል፡፡ ስለራሳቸው እና አካባቢያቸው ያላቸውን መረጃ በቃላት መሸምደድ ብቻ ሳይሆን በወረቀት ላይ ማስፈርም እንዲሁ፡፡ እርሳቸው ከመማራቸው በዘለለ ሌሎች እንዲማሩ በር ከፋች ሆነዋል፡፡ እናም ዛሬ ሕዝብ ሆይ ከእውቀት ገበታ ብትገናኙ መልካም ነው ሲሉም ይመክራሉ፡፡
የዱከም ከተማ መስተዳድር ትምህርት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ እሸቱ ዲንቃ፤ የጎልማሶች ትምህርት በ 2007 ዓ.ም እንደጀመረ ያስታውሳሉ፡፡ ይህ ሥራ ሲጀመርም በወቅቱ በመገናኛ ብዙሃን መረጃዎችን ለኅብረተሰቡ ማሰራጨት፤ ቋሚ ሠራተኞችን መቅጠር እና ብሎም ለትምህርት አመቺ ሁኔታዎችን ማመቻቸትን መሠረት ያደረገ ነበር፡፡ በመጀመሪያ ደረጃም ትምህርታቸውን የጀመሩ ወጣቶች ጥቂቶች ነበሩ፤ እናም የተሻለ ውጤት ያላቸውን ውጤታማ ተማሪዎች መሸለም አስፈላጊ መሆኑ ታመነበት፡፡
የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት የትምህርቱ አንድ አካል ሲሆን፤ የተሻለ ለውጥ ላመጡት ስልክ ተገዝቶ ተሰጣቸው፡፡ የሽልማቱ አንድምታም በአንድ በኩል ለማበረታት፤ በሌላ ጎኑ ደግሞ ሞባይል ስልክ መጠቀም መቻላቸውን ለማረጋገጥ ነበር ይላሉ፡፡ በትምህርታቸው ተላላፊ በሽታ መከላከል ስለሚቻልበት፣ የቤተሰብ ምጣኔና ያገኙትን ጥሪት መቆጠብ በሚቻልበት ምክር እና ትምህርት የተሻለ ለውጥ ማስመዝገብ እንደቻሉ ነው የሚናገሩት፡፡ በሂደትም በከተማ መስተዳድሩ ነዋሪ ከነበሩ አምስት ሺህ ያልተማሩ ጎልማሶች ውስጥ፤ ከግማሽ በላይ የተማረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 2 ሺ ወጣቶች ገና ከቀለም አልተዋወቁም፡፡ ይህንንም ለማቃለል ገና ብዙ መስራት አለብን ይላሉ፡፡
አቶ እሸቱ ለገሰ የቢሾፍቱ ከተማ ትምህርት ጽሕፈት ኃላፊ ናቸው፡፡ የተቀናጀ ጎልማሶች ትምህርት ሲጀመር በርካታ ውጣ ውረዶች እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡ ዘርፉን ባለቤትነት የሚመራ አካልና ሁኔታ አመቻች አልነበረም፡፡ ይሁንና ክልሉ መመሪያ እንዳወጣ አስፈላጊ ባለሙያዎች በቅጽበት በመቀጠራቸው ተገቢውን የሰው ኃይል በማሟላት ወደ ሥራ መግባት ተችሏል፡፡
በ2006 ዓ.ም የተማሩ ጎልማሶች 219 ብቻ ነበሩ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ይህ አሃዝ በእጅጉ ተመንድጎ ወደ 3ሺ368 ደረሰ፡፡ ይህም ከከተማ ካልተማሩ ስድስት ሺህ ጎልማሶች ውስጥ ሲሆን፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ 50 ከመቶ የሚሆነው ያልተማረው ነዋሪ ከቀለም ተዋውቋል ይላሉ፡፡
በወቅቱም የከተማ አስተዳደሩ ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪም ሌሎች ተቋማትን በር ማንኳኳት አስፈላጊ ነበር፡፡ በዚህም አዳማ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍ በማድረጉ ለውጡ በእጅጉ እያደገ መጣ፡፡ ዕድሜው ከ15 እስከ 64 ዓመት ሆኖት ያልተማረ ሰው እንዳይኖርም በተጀመረው ጥረት ስኬታማ ተግባር ማከናወን ተችሏል፡፡ በዚህም ተራማጅ አስተሳሰብ ያለው አርሶ አደር ለማፍራት፣ በምክንታዊነት የሚያምን ወጣት በማፍራት ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ ማንበብ እና መፃፍ ብሎም የአኗኗር ጥበባቸው በሳይንሳዊ መንገድ እንዲቃናም ጥበብ የሚፈጥር ትምህርት እንዲሆን በመደረጉ አርሶ አደሩ ላይ ለውጥ ማምጣት ችሏል፡፡ ቀደም ሲል በርካታ አርሶ አደሮችና ጎልማሶች ወደ ገበያ እና ሌሎች ግብይት ስፍራዎች ሲያመሩ ሂሳብ የሚያ ሰላላቸው አሊያም ደግሞ ድጋፍ የሚያደር ግላቸው ሰው ይፈልጋሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ነገሮች ተለውጠዋል፡፡ አርሶ አደሩ የራሱን ሕይወት በዘመናዊ መንገድ የሚመራበትን ዘዬ እየተከተለ ነው፡፡ ሥራው ወሳኝ በመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ ትልቅ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ ይህም አሁን ባለው የክልሉ ዕድገትና ተጨባጭ ሁኔታ እጅግ አስፈላጊና መጠናከር ያለበት እንደሆነ ነው አቶ እሸቱ የሚናገሩት፡፡
የምዕራብ አርሲ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከድር ኢለሞ ክልሉ ትምህርት በማስፋፋት ዘመቻው ስኬታማ ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ በገጠር አካባቢ የሚኖረው ማህበረሰብ ወደ ተሻለ ዕውቀትና አኗኗር ምዕራፍ እንዲሸጋገር የተቀናጀ የጎልማሶች ትምህርት አያሌ ለውጦችን እያመጣ ነው፡፡ ምንም እንኳን በዞኑ እየተመዘገበ ያለው ውጤት ከአምናው አኳያ ሲታይ መልካም ቢሆንም ተፈላጊው ግብ ላይ ግን እንዳልደረሰ ነው የሚናገሩት፡፡
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ለውጦቹ የሚያጓጉ እና በቀጣይም የበለጠ ለመስራት የሚያነሳሳ ነው፡፡ ከሕዝብ ጋር እየተደረገ ባለው ውይይትም ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ ነው፡፡ ወደ ትምህርት ቤት የመጣ ጎልማሳም ትምህርት ማቋረጥ ስለሌለበት በሰፊው ግንዛቤ የማስጨበጫ ሥራም እየተከናወነ ነው፡፡
አቶ ሸምሰዲን ኢብራሂም የምዕራብ ሐረርጌ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሲሆኑ፤ በዞኑ አብዛኛው ነዋሪ አርብቶ አደር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በዚህ ረገድ በጎልማሳ ትምህርት 15 የገጠር እና ሁለት የከተማ ወረዳዎች በመጀመር በርካቶችን ከመሃይምነት ቀንበር ማላቀቅ እንደተቻለ ይናገራሉ፡፡
በአሁኑ ወቅትም በዞኑም 72ሺ ሰዎች የተቀናጀ የጎልማሶች ትምህርት ለመቅሰም ተመዝግበው፤ 59ሺ የሚሆኑት በመማር ላይ ናቸው፡፡ ለውጡን የተገነዘቡ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸ ውንም ይጠቁማሉ፡፡ በዚህም በአራት ወረዳዎች ላይ ጎልማሳዎች ትምህርት ቤት በራሳቸው ተሳትፎ ገንብተው አስተማሪ ተቀጥሮላቸው በመማር ላይ ናቸው፡፡ ይህም ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ለሚገኙ በርካታ ወረዳዎች ምርጥ ተሞክሮ እየሆነ ነው፡፡
ይህን የሚመራ ቦርድ እና የቴክኒክ ኮሚቴ በመኖሩም መልካም ተሞክሮዎችንና ችግሮችን ለማየትም አሠራር ተዘርግቷል፡፡ በየሦስት ወሩም የሚገመገም ሲሆን፤ በየወሩ ሪፖርት ይደረጋል፡፡ ይህም አሠራር ከቀበሌ እስከ ክልል ድረስ የተሳሰረ መሆኑ ድጋፍ እና ክትትል ለማድረግም አመቺ ሁኔታዎችን ፈጥሯል፡፡ ይሁንና በዘርፉ ላይ የተመደቡ ባለሙያዎች በሚፈለገው ልክ ባለመስራታቸውና በገጠራማው አካባቢ የሚሰሩ ባለሙያዎች እጥረት በመኖሩ ስኬቱን እንዳያደበ ዝዝም ይሰጋሉ፡፡
አቶ ማሞ ቦጋለ የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሲሆኑ፤ ዜጎችን ከቀለም ጋር ለማስተዋወቅ በመደበኛ መማር ማስተማሩ ብቻ ማዳረስ አይቻልም፡፡ ስለሆነም ከመደበኛው ውጪ ሌላ ስትራቴጂ ተጀምሯል፡፡ ለዚህም የተቀናጀና ተግባር ተኮር የሆነ የጎልማሶች ትምህርት እየተሰራ ነው፡፡ ይህም አገሪቱ በቀጣይ ልታሳካቸው በምታስባቸው የማህበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ብሎም ፖለቲካዊ ብስለት እንዲኖራቸው የራሱ ሚና ይኖረዋል፡፡ ለዚህም ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ጀምሮ እስከ ታችኛው ድረስም አመቺ አሠራር ለመዘርጋት ተሞክሯል፡፡
ኅብረተሰቡም በሚገኘው እውቀት ከዕለት ተዕለት ኑሮው ጋር እንዲያሰላስለው ታስቦ የሚሰራ ነው፡፡ ለዚህም ያመች ዘንድ በገጠርም ይሁን በከተማ ሁለት አመቻቾች ተመድበው ሥራውን በማቀላጠፍ ላይ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ስኬቶች ቢኖሩም ከግብርናው እና ጤና ኤክስቴንሽን ዘርፍ ጋር በተፈለገው ልክ ቅንጅታዊ አሠራር ባለመኖሩ ተፈላጊው ውጤት ሳይመዘገብ ቆይቷል፡፡ ይህም መስተካከል ስላለበት አዲስ መመሪያ ተዘጋጅቶ ሥራው ተጀምሯል፡፡ በዚህ መመሪያ ላይም ከፍተኛ ንቅናቄ ለመፍጠር ታስቧል ይላሉ፡፡ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችም ትልቅ ትኩረት ስለሠጡት የተሻለ ሥራ እንደሚከናወን ይገልፃሉ፡፡
በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ በበኩላቸው ፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ብሎም በክልሉ ከፍተኛ የሆነ ያልተማረ ሰው ይገኛል፡፡ በመሆኑም ማሕበረሰቡ ከእውቀት አድማስ ርቆ የሚኖርበት ጊዜ ማብቃት እንዳለበት በመታመኑ እንደ አገር ብሎም እንደ ክልል ሰፊ ዘመቻ እየተደረገ እንደሆነ ነው የሚያብራሩት፡፡ በዚህም በርካታ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በተግባር ተኮር ትምህርት እራሳቸውን ከመቻላቸውም በዘለለ ለሌሎች እገዛ እና ድጋፍ ማድረግ ችለዋል፡፡ በዚህም እየመጣ ያለው ለውጥ ተስፋ ሰጪ በመሆኑ ባለሙያዎችንና በቂ ሀብት በመመደብና ወደሥራ በማሰማራት ትልቅ ግብ ለማስመዝገብ ታቅዷል፡፡ ለዚህም የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

Published in ማህበራዊ
Monday, 05 February 2018 16:48

የአሠራር ለውጥና ውጤቱ

የሰነድ ማረጋገጥ ተግባራት ሰነዶችን የማረጋገጥና የመመዝገብ፣ የሰነድ ቅጅዎችን ከዋናው ጋር በማመሳከር ትክክለኛነታቸውን የማረጋገጥና የመመዝገብ፣ ቃለ መሃላና በቃለ መሃላ የሚሰጡ ማረጋገጫዎችን የመቀበልና የመመዝገብ፣ ባለጉዳዮች ሲጠይቁ እንደ አስፈላጊነቱ የፊርማ ወይም የማህተም ናሙና የመያዝ፣ ለመረጋገጥ በሚወርዱ ሰነዶች ላይ የሚፈርሙ ወይም የፈረሙ ሰዎችን ችሎታ፣ መብትና ሥልጣን የማረጋገጥ፣ ለመረጋገጥ የሚቀርቡ ሰነዶችን ሕጋዊነት የማረጋገጥ፣ በሕግ የባለቤትነት ማረጋገጫ የሚሰጥባቸው ንብረቶችን ለማስተላለፍ በሚደረጉ ውሎች፣ የንብረት አስተላላፊውን ባለመብትነትና ንብረቱ በመያዣነት ያልተሰጠ ወይም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ያልታገደ መሆኑን የማረጋገጥ፣ ስለተረጋገጡና ስለተመዘገቡ ሰነዶች ሥልጣን ባለው አካል ሲጠየቅ ማስረጃ የመስጠት፣ እና ሌሎች ተመሳሳይ ተግባራትን ይይዛል፡፡
በየትኛውም የዓለም ሀገሮች እንዳለው ሁሉ በአገሪቱም ሰነዶች የማረጋገጥ፣ የመመዝገብ እና የማስቀመጥ ሥራ የተጀመረው በሀገሪቱ ዘመናዊ ሕጎች ከመቀረፃቸውና ተግባር ላይ ከመዋላቸው በፊት ሲሆን ይኼውም በተለያዩ ደረጃ ተግባራዊ ሲደረግ እንደነበር የተለያዩ ታሪካዊ ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡ ከ1930ዎቹ ጀምሮ ለተወሰነ ጊዜ በግለሰቦች ተይዞ ሲሰራ ከቆየ በኋላም ሥራውን የሚያከናውን ተቋም የውል ክፍል፣ የውል ዋና ክፍልና የመሳሰሉት ስያሜዎች እየተሰጠው በከፍተኛ ፍርድ ቤትና በአውራጃ ፍርድ ቤት፣ በፍትህ ሚኒስቴር ወይም በህግና ፍትህ ሚኒስቴር ሥር ሆኖ ሥራውን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
የኢፌዴሪ የመንግሥት አካላት ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 8/1980 የፍትህ ሚኒስቴር የውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽ/ቤቶችን የማደራጀትና በበላይነት የመቆጣጠር ሥልጣን እንደተሰጠውና በዚሁ ስር ተደራጅቶ እንደነበር፣ በ1985 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 41/1985 መሰረት ጽህፈት ቤቱ ከፍትህ ሚኒስቴር ወጥቶ በቀድሞ የክልል 14 መስተዳድር የፍትህ ቢሮና የክልል ፍርድ ቤት ስር ተዋቅሮ መደራጀቱ፣ ከ1988 ሚያዝያ ወር ጀምሮ ደግሞ በማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 26/1993 ራሱን ችሎ በጽህፈት ቤት ደረጃ ተዋቅሮ የውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽህፈት ቤት በመባል ተጠሪነቱ ለአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሆኖ አገልግሎቱን ሲሰጥ መቆየቱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በ1995 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን በአዲስ መልክ ለማደራጀት በተደረገው እንቅስቃሴ ቀደም ሲል በህግ ተቋቁሞ ሲሠራ የነበረው “የውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽህፈት ቤት” በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር በክፍል ደረጃ ለመስተዳድሩ ጽህፈት ቤት ተጠሪ ከነበረው የልደትና ጋብቻ ምዝገባ አገልግሎት ጋር በመቀላቀል ”የውልና የክብር መዝገብ ማስረጃ አገልግሎት” በሚል ስያሜ እንዲደራጅ በከተማው የአስፈፃሚና የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት አካላት ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 2/1995 መሠረት ተወስኖ ራሱን የቻለ ህጋዊ ተቋም ሆኖ በምክር ቤቱ በጀት ተመድቦለትና በካቢኔው ኃላፊ ተሹሞለት እስከ ሰኔ 1998 ዓ.ም በዚሁ መልክ ሲሠራ ቆይቷል፡፡
የሰነዶች ማረጋገጥና ምዝገባ ሥራ በመላ አገሪቱ ተፈፃሚነት የሚኖረው አንድ ወጥ የፌዴራል ህግ ቢመራ በዜጐች መካከል የሚከናወኑ የንግድና ሌሎችንም የኢኮኖሚ እና ህጋዊ ግንኙነቶች በማቀላጠፍ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን በመታመኑ ይህንኑ ሥራ የሚያከናውኑ ተቋማትን ተግባርና ኃላፊነት በህግ በመደንገግ አዋጅ ቁጥር 334/1995 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመውጣቱ የአሁኑ ተቋም በአዋጁ መሠረት የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽህፈት ቤት ተብሎ እንዲሰየም አደረገ፡፡
ከላይ የተጠቀሰው አዋጅ በ1995 ዓ.ም አጋማሽ ፀድቆ በነጋሪት ጋዜጣ ቢወጣም ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባር ሳይገባ እስከ 1997 ዓ.ም ከቆየ በኋላ በማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 467/1997 መውጣት ምክንያት አዋጁ ወደ ተግባር መለወጥ እንቅስቃሴ በመጀመር ተጠሪነታቸው ለየከተማው መስተዳድር ምክር ቤቶች ተደርገው እንዲቋቋሙ በአዋጁ ታስበው የነበሩ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽህፈት ቤቶች ተጠሪነታቸው ለፌዴራል ፍትህ ሚኒስቴር ሆኖ በአዋጁ የተዘረዘሩትን ተግባራት እንዲያከናውኑ ተደረገ፡፡ ለአሠራር እንዲያመች ተጠሪነቱ በቀጥታ ለፍትህ ሚኒስቴር እንዲሆን በአዋጁ ላይ የተቀመጠለት የድሬዳዋ ጽህፈት ቤትም ተጠሪነቱ አዲስ አበባ ለሚገኘው የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽህፈት ቤት እንዲሆን በደብዳቤ መመሪያ በመሰጠቱ እንደ አንድ የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሆኖ መስራት ጀመረ፡፡
የሰነዶች ማረጋገጥና ምዝገባ ሥራው በዚህ መንገድ ይጓዝ እንጂ በአሰራር ደረጃ ኋላቀርና የመልካም አስተዳደር ችግሮች የነበሩበት ነበር፡፡ ይህንንም ለመለወጥ የተለያዩ እምርጃዎች ተወስደዋል፡፡ የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ ኤጀንሲው ቀድሞ ከነበረበት ኋላቀር አሰራር ተነስቶ አሁን ከደረሰበት ጥራት ያለው አሰራር እንደደረሰ ከዝግጅት ክፍሉ ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ ተናግረዋል፡፡ ዝርዝሩን እንደሚ ከተለው አቅርበነዋል፡፡
የነበሩ ችግሮች
የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ቀደም ሲል በተለያዩ አጠራር ሲጠራና በተለያየ አደረጃጀት ሲንቀሳቀስ የነበረ ተቋም ነው፡፡ በተለይ ከ1985 ዓ.ም በኋላ በተለያዩ አደረጃጀቶች ማለትም በፍርድ ቤት ስር ሆኖ እንዲሁም በቀድሞ ፍትህ ሚኒስቴር ስር ሆኖ እንደ አንድ የሥራ ክፍል ሆኖ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ ተቋም ነው፡፡ በ1990 ዓ.ም መግቢያ አካባቢ የተቋሙ መገለጫ ከነበሩ ጉዳዮች አንዱ የመልካም አስተዳደር ችግር ነበር፡፡ ከተደራሽነትም አንፃር በአንድ ማዕከል ብቻ ነበር አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው እንዲሁም አገልግሎት የመስጠት ብቃቱ በራሱ በቀን ለጥቂት ተስተናጋጆች ብቻ ነበር፡፡ በጣም ውስብስብና ከአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ጥራትም አንፃር በርካታ ችግሮች የነበረበት ተቋም ነበር፡፡ በተለይ በአንድ ማዕከል አገልግሎት ከመስጠት ጋር ተያይዞ ሌሊት ጭምር ወረፋ ሲያዝበት የነበረ ተቋም መሆኑ ከሃያ ዓመት በፊት የነበሩ ታሪኮች ያሳያሉ፡፡
የለውጥ ጅማሮ
በ1990 ዓ.ም መጀመሪያ መንግሥት የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራምን ተግባራዊ ማድረግና ማስተዋወቅ በጀመረበት ጊዜ ተቋሙ በራስ ተነሳሽነት የተለያዩ ለውጦችን ማካሄድ ጀመረ፡፡ ለለውጥ መነሻ ሆኖ የነበረው ዋናው የመልካም አስተዳደር ችግር ነበር፡፡ ይህን ለማድረግ የመጀመ ሪያው በወቅቱ የነበረው አመራርና ሠራተኛ ተቋሙ ባለው አካሄድና አስተሳሰብ ተገልጋዩን ማርካት ባለመቻሉ ለውጥ ካልተደረገ ተቋሙ መቀጠል አይችልም የሚል የጋራ አቋም ላይ መድረሳቸው ነበር፡፡ በዚህም ሠራተኛውና አመራሩ በጋራ የነበሩትን ችግሮች ወደ መለየት ሥራ ገቡ፡፡ የችግሮቹን ምንጭ በመለየት እንዴት ሊፈቱ እንደሚችሉ አቅጣጫ አስቀመጡ፡፡
ከተለዩት ችግሮች ውስጥ የአስተሳሰብ፣ የአደረጃጀት እንዲሁም ከአሠራር አንፃር የተስተዋሉትን ቅድሚያ ሰጡ፡፡ በአስተሳሰብ ሲባል ሠራተኛው ላይ የነበረው አስተሳሰብ ከሰው ኃይል ቁጥር ማነስ ጋር ተያይዞ የተከሰተ ነበር፡፡ ይህም ለለውጥ ተነሳስሽነትን በመፍጠር የአሰራር ለውጥ ለማምጣት መነሻ ሆነ፡፡ ባለው የሰው ኃይል መለወጥ እንደሚቻል በተግባር ማሳየት ከተቻለ በኋላ ነበር የመንግሥት ድጋፍ የተጠየቀው፡፡ በዚህም ቀላል በሚባል ሁኔታ ለውጥ ማምጣት ተቻለ፡፡
ከለውጥ ሥራዎቹ ውስጥ የመጀመሪያው ግልፀኝነ ትን ለማስፈን የተጀመረው ሥራ ነው፡፡ አገልጋዩ ማን እንደነበር የማይታወቅ ስለነበር የደረት ባጅና የጠረጴዛ ባጅ እንዲዘጋጅ ተደረገ፡፡ በዚህ አሰራር ሠራተኛው ተጠያቂነትን እንደ ሚያመጣ እየተገነዘበ ሄደ፡፡ ይህንን መሰረት አድርገው ሠራተኛው መለወጥና የአገልጋይነት መንፈስ ማምጣት ሲጀምር አላሰራ ብሎ የነበረው አደረጃጀት እንዲጠና ተደረገ፡፡ ከጥናቱ በኋላ በአዲስ አበባ አስተዳደር ስር ሥራውን ማከናወን ቀጠለ፡፡
ከአሠራር አንፃር ከነበሩ ችግሮች ውስጥ ሌላው ብዙ ጊዜ ውሳኔዎች በአንድ ሰው ወይም በተቋሙ የበላይ ኃላፊ ብቻ የሚሰጡበት ሁኔታ መኖሩ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት አገልግሎት መስጠቱ በጣም አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ የሠራተኛው የአገልጋይነት አስተሳሰቡ ከተፈጠረ በኋላ የሠራተኛውን አቅም የማምጣት ሥራ ተሰርቶ አንድ ቦታ ላይ የነበረውን ውሳኔ ወደ ታች እንዲወርድ ተደረገ፡፡ ከዚህ በኋላ ውሳኔዎች በያሉበት እንዲፈፀሙ የማድረግ ሥራው ተጀመረ፡፡ ለዚህም ደግሞ ተከታታይነት ያለው የአቅም ግንባታ ሥራ ተሰርቷል፡፡ በዚህ መሠረት በ1994 ዓ.ም ተቋሙ ከነበረበት የመልካም አስተዳደር ችግር በከፍተኛ ሁኔታ ለውጥ የታየበት ሄደ፡፡
ይህ ሲሆን የሌላውን ሠራተኛ ተነሳሽነት እያመጣ ሄደ፡፡ በዚህም ሠራተኛው ‹‹ትንሽ ሰርተን ይህን ማግኘት ከቻልን ብዙ በመስራት የበለጠ መመስገን ሊመጣ ይችላል›› የሚል አስተሳሰብ በውስጡ መፍጠር ቻለ፡፡ ይህንን መሠረት አድርጎ በወቅቱ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራም ውስጥ አንደኛው የአገልግሎት ማሻሻያ እንደመሆኑ ተቋሙ እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ አገልግሎትን አሻሻለ፡፡
ተቋሙ በአዲስ አበባ አስተዳደር ስር እንዲሆን ከተደረገ በኋላ የተገልጋዩ ቁጥር እየጨመረ መጣ፡፡ ቀድሞ በቀን 30 ሰዎች ብቻ ነበር ማስተናገድ የሚቻለው፡፡ ከለውጥ በኋላ ግን ቅርንጫፎች የማስፋት ሥራዎች ተከናወኑ፡፡ በ1998 ዓ.ም ወደ ፍትህ ሚኒስቴር ተጠሪ ከሆነ በኋላ እንደ አንድ የፌዴራል መንግሥት የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት በመባል እንዲጠራ ተደረገ፡፡ ከዚህ በኋላ አገልግሎት እየሰጠ ሕዝቡ ከመንደር ውል በመላቀቅ በውል አዋዋይ ወገን ህጋዊ ውልን የመዋዋል ፍላጎት እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የተቋሙ ተገልጋዮች በርካታ እየሆኑ መጡ፡፡
ተቋሙ የአገልግሎት አድማሱን በማስፋትና ተደራሽ ለመሆን በ2000 ዓ.ም አካባቢ ሁለት ቅርንጫፍ ብቻ የነበሩት ሲሆን ቅርንጫፎችን ለማስፋት ባደረገው ሥራ በ2004 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ በአዲስ አበባ የቅርንጫፍ ቁጥሩን አምስት አደረሰ፡፡ በወቅቱ በቀን አንድ ሺ አምስት መቶ ተገልጋይ ማስተናገድ ቻለ፡፡ በ2006 ዓ.ም መጨረሻ የቅርንጫፍ ቁጥሩ አስር በማድረስ የተገልጋዩ ቁጥር በቀን ወደ ሦስት ሺ እንዲያድግ አድርጎታል፡፡ አሁንም የተገልጋዩ ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ባሉት ቅርንጫፎች አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ ባለመቻሉ አዳዲስ ቅርንጫፎች መክፈትና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለመጠቀም ዝግጅት ተደረገ፡፡ ተቋሙ አሁን ያሉትን የተለያዩ ውክልናዎች፣ የተለያዩ የስምምነት ሰነዶች በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ አደረገ፡፡
በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት መስጠት
በ2004 ዓ.ም ላይ የውክልና ሥራዎች ተገልጋዩ ባለበት ቦታ በቀጥታ በኢንተርኔት አገልግሎት መስጠት ተጀመረ፡፡ ሰዎች ባሉበት ሆነው መረጃቸውን እየሞሉ በቀላሉ ሊገለገሉበት የሚችሉ ሥርዓትን ተቋሙ መፍጠር ቻለ፡፡ የቴክኖሎጂ ሥራውን በማስፋት የተለያዩ የንግድ ውሎች ወይም ንብረት የማስተላለፍ ውሎች ማለትም በስጦታና በሽያጭ የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይን ቀሳቀስ ንብረት ለማስተላለፍ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት የመስጠት አሠራር ተዘረጋ፡፡
አሁን ያሉት የቅርንጫፎች ብዛት በአዲስ አበባ 14 ሲደርስ በድሬዳዋ አንድ ቅርንጫፍ አለ፡፡ በእነዚህ ቅርንጫፎች በቀን ከአምስት ሺ ስድስት መቶ በአማካይ ተገልጋይ እየተስተናገደ ይገኛል፡፡ ሌላው በ2004 ዓ.ም አካባቢ እንደ መልካም አስተዳደር ችግር ተለይቶ የነበረው አገልግሎት አሰጣጥ ቅድሚያ የመጣ ቅድሚያ ይስተናገዳል የሚል ነበር፡፡ ከህዝብ መብዛት ጋር ተያይዞ ክፍተቶች ነበሩ፡፡ ይህም የሆነው ተራ የማስከበር ሥራው በሰዎች የሚከናወን በመሆኑ ነበር፡፡ ይህንን በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ ተደርጎ የወረፋ ማስጠበቂያ ሲስተም ተግባር ላይ ውሏል፡፡
አስራ አራቱም አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙት ቅርንጫፎች በቴክኖሎጂ የተገናኙ ናቸው፡፡ የሰነድ አደረጃጀቶች በኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ስለተገናኙ ተገልጋዩ በፈለገው ጊዜ በቀላሉ ሊገኝ በሚችልበት ሁኔታ ተቀምጧል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በቀጣይ ሰነዶችን ያለ ዲጅታል መሣሪያ ማስቀመጥ እንደማይቻል መረዳት ይቻላል፡፡ ለዚህም ሰነዶች በዲጅታል መንገድ እንዲዘጋጁ የማድረግ ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡
ከክልሎች ጋር ያለው ግንኙነት
ኤጀንሲው እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው በፌዴራል ደረጃ ሲሆን ይህ ደግሞ አዲስ አበባንና ድሬዳዋን ብቻ ያካተተ ነው፡፡ በ2008 ዓ.ም የተቋሙ አዋጅና የተቋቋመበት ደንብ እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡ በደንቡ ላይ ይህ ተቋም የተሰጠው ሥልጣን ወደ ኤጀንሲነት ሲያድግ በፌዴራል ደረጃ ሰነድ የማፅደቅና የማረጋገጥ ሥራ ነው፡፡ ክልሎች ደግሞ በራሳቸው ሰነድ የማረጋገጥና የመመዝገብ ሥልጣን አላቸው፡፡ ተቋሙ ግን ክልሎች የመደገፍ፣ የማስተባበር፣ አቅም የመፍጠር እንዲሁም ከዚህ በዘለለ አንድ ወጥ የሆነ የመረጃ ግንኙነት እንዲፈጠርና መረጃዎች አንድ ቦታ እንዲሆኑ እንዲሁም አሠራሮች ወጥነት ባለው ሰነድ የማረጋገጥና የመመዝገብ አገልግሎትን እንዲሰጥ የማስተባበርና ድጋፍ የማድረግ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ነገር ግን በክልል ደረጃ ቅርንጫፍ ከፍቶ እራሱ ሰነድ የማረጋገጥና የመመዝገብ ሥራ አያከናውንም፡፡ ኤጀንሲው በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ላይ ብቻ ሥራዎችን ይሰራል፡፡
በአራቱ ክልሎች ማለትም በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ያሉት ክፍተቶች እንዲጠኑ ተደርጓል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመትም አቅም ከመፍጠር ጋር ያሉትን ክፍተቶች ለመሙላት ከየክልሉ ስምንት ሰዎችን በመመልመል ወጥነት ያለው ሰነድ የማረጋገጥና የመመዝገብ አገልግሎት እንዲኖር በተቋሙ አሠራር ላይ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ በየክልሉ የተበታተነው አደረጃጀትም ወጥነት እንዲኖረው ለማድረግ በጋራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ አደረጃጀቶቹ መስተካከል ከቻሉ በአሠራር ደረጃ ክልሎችም የኤጀንሲውን አሠራር እየተከተሉ ይሄዳሉ፡፡
የተገልጋይ እርካታ
ተቋሙ በዓመት አንድ ጊዜ ዝርዝር የተገልጋይ ጥናት ያካሂዳል፡፡ በየጊዜው ደግሞ በአስተያየት መስጫና መዝገቦች የሚሰጡ አሉ፡፡ እነዚህን መሠረት በማድረግ በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ ከስምንት ሺ በላይ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። ከዚህ ውስጥ 91 በመቶው እርካታ አግኝተዋል፡፡ የቀሩት ደግሞ መሻሻል አሉባቸው ያሉዋቸውን የጠቆሙ ተገልጋዮች ናቸው፡፡ ቴክኖሎጂ መጀመሪያ ሲጀመር ቀስ በቀስ ነው የሚለመደው፡፡ በቅርቡ የተጀመረው የሚን ቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች የማስተላለፍ ውል ላይ በቴክኖሎጂ የመጠቀም ሥራ ስለሆነ እዚህ ላይ የሠራተኛው መስራት ፍጥነት ዝቅ ያለ በመሆኑ ተገልጋዩ ቅሬታ ያቀርባል፡፡ ተቋሙም ለተገልጋዩ ከፍጥነት በላይ ጥራት አስፈላጊ መሆኑን ግንዛቤ እየሰጠ ይገኛል፡፡
በቅርንጫፍ ሦስት መገናኛ አካባቢ በሚገኘው የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ያገኘናቸው አቶ ከድር አሊ፤ በንግድ ሥራ ለረጅም ዓመታት መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ የተለያዩ ንብረቶቻቸውን በውክልና ለመስጠትና ውሎችን ለመዋዋል ኤጀንሲውን ሲጠቀሙ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ኤጀንሲው ቀደም ብሎ ይሰጠው የነበረው አገልግሎት ኋላቀርና አንድ ቦታ ላይ ብቻ በመሆኑ በፍጥነት የሚፈልጉትን ለማግኘት ይቸገሩ እንደነበር ይናገራሉ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኤጀንሲው በተለያዩ ቦታዎች ቅርንጫፎችን በመክፈት እየሰጠ ያለው አገልግሎት ከእንግልት እንዳዳናቸውና የሚፈልጉትን ጉዳይ በቴክኖሎጂ በታገዘ መንገድ ስለሚያከናውንላቸው ደስተኛ መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡ በቀጣይም ኤጀንሲው አሠራሩን ዘመናዊ በማድረግ ቀልጣፋ አሠራሩን መቀጠል እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡
ሌላው አስተያየት የሰጡን ስድስት ኪሎ በሚገኘው በቅርንጫፍ አራት የቤት ውክልና ለመስጠት የመጡት አቶ ዘነበ ወንድሙ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ ቀድሞ የነበረው የሰነድ ማረጋገጫና ምዝገባ ሥርዓት ተገልጋዩን ያላማከለ ከመሆኑ ባሻገር ኋላቀር አሠራር የነበረው ነው፡፡ ሠራተኞቹም የሚሰጠት አገልግሎት በቀን ለውስን ሰዎች በመሆኑ አገልግሎት ለማግኘት ወራት ይፈጁ ነበር፡፡
ኤጀንሲው አሠራሩን ዘመናዊ በማድረግና በተለያዩ ቦታዎች ቅርንጫፍ ከፍቶ እየሰጠ ያለው አገልግሎት አስደሳች እንደሆነና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ በመሆኑ ቀድሞ የገቡ ውሎች ይሁን ሰነዶች በቀላሉ ማግኘት እንደሚቻል ይጠቁማሉ፡፡ በቀጣይ ዘመናዊ አሠራሮችን በማሳደግ የሰነድ ማረጋገጡና ምዝገባ ሥርዓቱ ይበልጥ ቀልጣፋ እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት ያመለክታሉ፡፡
በአገራችን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በርካታ ተቋማት የመልካም አስተዳደር ምንጭ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡ እነዚህ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ደግሞ ተጠራቅመው ሀገራዊ አለመረጋጋትን ይፈጥራሉ፡፡ እነዚህን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት በቅድሚያ የችግሮቹን ምንጭ መለየት ደግሞ ተገቢ ነው፡፡ የፌዴራል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲም ቀደም ሲል የነበሩበትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት የሄደበት መንገድ አስተማሪነት ያለው ነው፡፡ እናም እያንዳንዱ ተቋም በተለይ የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚነሳባቸው ተቋማት ከዚህ ተሞክሮ በመውሰድ ራሳቸውን መፈተሽና ችግሮቻቸውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመፍታት ለኅብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዛሬ ያልተፈታ ችግር ነገ የገዘፈ የሀገር ችግር ሆኖ እንዳይወጣም መፍትሄው ራስን መፈተሽ ነውና፡፡

መርድ ክፍሉ

Published in ፖለቲካ

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በከተሞች የመንግሥት ዋና ትኩረት ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ሥራ አጥነትንና ድህነትን መቀነስና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች እኩል ተጠቃሚ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የሥራ ፈጣሪነት አስተሳሰብና ዕውቀትን በማዳበር ዜጎች የራሳቸውን ሥራ በመፍጠር ለአገሪቱ ቀጣይ የኢንዱስትሪ ልማት መሠረት እንዲሆኑ ማድረግም የትኩረት አቅጣጫው ማጠንጠኛ ነጥብ መሆኑ ተመላክ ቷል፡፡ በተለዩት የትኩረት አቅጣጫዎች መሠረት ግቦች ተቀምጠው ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ ዕቅዱን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን ያስችል ዘንድም ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ጉዳዩን በባለቤትነት የሚመራ ራሱን የቻለ የመንግሥት አካል ተቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ለዚህ ሥራ ኃላፊነት ተሰጥቶት ወደ ሥራ የገባው የፌዴራል የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲም ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን በከተሞች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ሊተገበሩ ይገባል ተብለው በመንግሥት የተለዩ የትኩረት መስኮችን ተከትሎ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በዛሬው ጽሑፋችን በዕቅድ ዘመኑ በከተሞች ከተቀመጡ የትኩረት አቅጣ ጫዎች መካከል በምግብ ዋስትና ዘርፉ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን እንዳስሳለን፡፡
በዚህ ዘርፍ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት እየተከናወኑ ከሚገኙ ሥራዎች መካከል አንደኛው በዕቅድ ዘመኑ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ በተመረጡ አስራ አንድ ከተሞች ውስጥ ለሚኖሩ ከ604 ሺ በላይ የሚሆኑ የድሃ ድሃ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተተገበረ የሚገኘው የከተሞች የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር ነው፡፡ የፌዴራል የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የ2010 በጀት ዓመት የመጀመሪያ መንፈቀ ዓመት አፈጻጸሙን ሰሞኑን በአዳማ በገመገመበት መድረክ ወቅት የተገኙት የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ቢራሳ እንደገለጹት፤ መርሃ ግብሩን ዕውን ለማድረግ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል፡፡ በዚህም በመጀመሪያው ዙር የትግበራ ምዕራፍ ከአስራ አንዱም ከተሞች ማለትም ከአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ መቀሌ፣ ሰመራ፣ ደሴ፣ አዳማ፣ ጅግጅጋ፣ አሶሳ፣ሃዋሳ፣ ጋምቤላና ሐረሪ የተመረጡ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ አንድ መቶ ዘጠና ሺህ ዜጎችን በአካባቢ ልማት ሥራዎች በማሳተፍና በቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ይናገራሉ፡፡ በተያዘው የበጀት ዓመትም በሁለተኛ ዙር በሰባት ከተሞች (አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ መቀሌ፣ ደሴ፣ አዳማ፣ ጅግጅጋ፣ ሃዋሳ) ከድህነት ወለል ስር በታች የሚኖሩ 210 ሺ 743 የድሃ ድሃ ዜጎችን የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ ለማድረግ ያልተቋረጠ የድጋፍና ክትትል ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም የምልመላ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ይህም የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ ዜጎችን በአካባቢ ልማት ሥራዎች በማሳተፍና የሥራ ዕድል የሚፈጥሩበትን መንገድ በማመቻቸት የምግብ ዋስትና ተጋላጭነታቸው የሚቀንስበት ሁኔታ እንዲፈጠር ያግዛል፡፡ ከእነዚህ በሁለተኛው ዙር የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር ተጠቃሚ ዜጎች መካከል 68 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ በመንፈቅ ዓመቱ በተከናወኑ የትግበራ አፈጻጸም ሂደቶች ውስጥ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተሰሩ ሥራዎች አበረታች ውጤት የታየባቸው ቢሆንም የተቀመጠውን ግብ በተሟላ መልኩ ለማሳካት የሴቶችን ልዩ ሁኔታ ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ በቂ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ ያመላከቱት፡፡
የፌዴራል የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የስትራቴጅክ ዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሪት መነን መለሰ በበኩላቸው መንግሥትና የዓለም ባንክ በተስማሙት መሠረት የምግብ ዋስትና መርሃ ግብሩ በመላ አገሪቱ በተመረጡ አስራ አንድ ከተሞች በሦስት ዙር ተከፍሎ ለአምስት ዓመታት የሚተገበር ነው፡፡ የመጀመሪያው ዙር በ2009 ዓ.ም 190 ሺ ዜጎችን ተጠቃሚ በማድረግ ተተግብሯል፡፡ እንደ ወይዘሪት መነን ገለጻ በተያዘው 2010 የበጀት ዓመት የሁለተኛው ዙር ተጠቃሚዎች ብዛትም በተመሳሳይ 190 ሺህ ሆኖ በሰነዱ ላይ የተቀመጠ ቢሆንም በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የድህነት መጠን በፍጥነት ለመቀነስ ከዓለም ባንክ ጋር በተደረገ ድርድር ተጨማሪ 60 ሺህ 885 ዜጎችን ከአዲስ አበባ ተጠቃሚ ለማድረግ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ 250 ሺህ 885 ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ከአስራ አንዱ ከተሞች መካከል በሰመራ፣ አሶሳ፣ ጋምቤላና ሐረር የምግብ ዋስትና መርሃ ግብሩ በመጀመሪያው ዙር ተጠናቋል፡፡ በመሆኑም ሁለተኛው ዙር የዘንድሮው የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር የሚተገበረው በቀሩት ሰባት ከተሞች ብቻ ይሆናል፡፡ እነዚህም ከተሞች አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ መቀሌ፣ ደሴ፣ አዳማ፣ ጅግጅጋና ሃዋሳ ናቸው፡፡
የከተሞች ዝግጅት ያለበት ደረጃ
የሁለተኛው ዙር የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር የሚተገበርባቸው ከላይ የተጠቀሱት ሰባቱ ከተሞች ከፌዴራሉ የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ባለፉት ስድስት ወራት የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በዚህም መርሃ ግብሩን ለሚያስተባብሩ የከተሞች አመራሮችና ባለሙያዎች በኤጀንሲው በኩል የአሰልጣኞች ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግ ስልጠናውን የወሰዱ አመራሮችና ባለሙያዎች በበኩላቸው በየከተማው ለሚገኙ የቀጣና የተጠቃሚዎች መልማይ ኮሚቴዎችና ባለ ድርሻ አካላት ተግባር ተኮር ስልጠና ከተሰጠ በኋላ የነዋሪዎች የቤት ለቤት ምዝገባና የተጠቃሚዎች ምልመላ ተከናውኗል፡፡ ከየከተሞቹ የቤተሰብ ናሙና በመምረጥ ቅድመ የኑሮ ደረጃ ምዘናና ጥናት በማከናወን ምልመላና መረጣ ተካሂዷል፡፡
በኤጀንሲው የመንፈቅ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ላይ እንደተመላከተው ከከተሞች መካከል በአዳማና በድሬዳዋ የኑሮ ደረጃ ምዘና ጥናቱ ተጠናቆ ውጤቱ እየተጠበቀ ይገኛል፡፡ በጅግጅጋ ከተማ የኑሮ ምዘና ጥናቱ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በአዲስ አበባ በአስሩም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ሃምሳ አምስት ወረዳዎችና በተመረጡ ቀጣናዎች አምስት የድጋፍና ክትትል ቡድን ተቋቁሞ ከቀጣና ኮሚቴዎች ጋር በመተባበር ለሰባት ተከታታይ ቀናት የነዋሪዎች የቤት ለቤት ምዝገባ ሥራ ተሰርቷል፡፡ ምዝገባው በዚህ መልኩ ከኤጀንሲው የድጋፍና ክትትል ቡድን ጋር በመተባበር መሰራቱም በምዝገባ ሂደቱ ይስተዋሉ የነበሩ ግድፈቶች ሳይውሉ ሳያድሩ እዚያው በምዝገባ ቦታው ላይ እንዲስተካከሉና ተገቢው የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ አስችሏል፡፡ የተጠቃሚዎች ምልመላና መረጣ ሥራ ተጠናቆ ውጤት እየተጠበቀ ይገኛል፡፡ በቀሪዎቹ አራት ከተሞች ማለትም በሃዋሳ፣ ደሴ፣ ድሬዳዋና መቀሌ ደግሞ የኑሮ ምዘና ጥናቱን ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ይህንን ሁለተኛውን ዙር የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር ኅብረተሰቡን በንቃት በማሳተፍ በተሟላ መልኩ ለመተግበር እንዲቻል በሰባቱም ከተሞች ከኅብረተሰቡ የተውጣጣ የምልመላና የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ተደራጅቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡
የተጠቃሚዎች የሥራ አደረጃጀት
የምግብ ዋስትና መርሃ ግብሩ ሁለት ዓይነት ተጠቃሚዎች ይኖሩታል፡፡ ይኸውም መርሐ ግብሩ ተግባራዊ እየተደረገባቸው በሚገኙ አስራ አንዱም ከተሞች መስራት የሚችሉ ተጠቃሚዎችን በአካባቢ ልማት ሥራዎች እንዲሳተፉ በማድረግ ሲሆን ሁለተኛው መንገድ ደግሞ በልዩ ልዩ ችግሮች ምክንያት መስራት ለማይችሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ በቀጥታ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም በአካባቢ ልማት ተሳታፊ የሆኑ ተጠቃሚዎች በሁሉም ከተሞች በአንድ ለአምስትና በአንድ ለሰላሳ ቡድን እንዲደራጁ በማድረግ ለየቡድኖቹ ሰብሳቢዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ በመስጠትና የአሠራር መለኪያዎችን በማስቀመጥ በሥራቸው ዙሪያ ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች ራሳቸው መፍትሄ እየሰጡ መሄድ የሚችሉበት አሠራር ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ መስራት የሚችሉ የመርሃ ግብሩ ተቃሚዎች የሚሰማሩባቸው የአካባቢ ልማት ሥራዎችም የተለዩ ሲሆን፤ እነዚህም የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት፣ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ፣ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት፣ መሠረተ ልማት ግንባታና የከተማ ግብርና ናቸው፡፡ የፋይናንስ ፍሰትና ግብዓት አቅርቦትን በተመለከተም በበጀት ዓመቱ በሁሉም የፕሮጀክቱ ማዕቀፎች የበጀት ድልድል ተሰርቶ ለከተሞች እንዲዳረስና ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡

 ይበል ካሳ

Published in ኢኮኖሚ

ባለፉት ሦስት ዓመታት በየመን ውስጥ በተከታታይ የነበረው የርስበርስ ጦርነት እጅግ የከፋ ከመሆኑ ባሻገር ወደ ከፍተኛ መከፋፈል ደረጃ መድረሱን አልጀዚራ በድረገፁ ያሰፈረው መረጃ ያሳያል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንትም ለመንግሥት ታማኝ የሆነው የጦር ኃይል ፕሬዚዳንት አብዱ ራቡ ማንሶር ሀዲን ከሳውዲ አረቢያ ይዞ ተመልሷል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በደቡባዊት የመን ወደምትገኘው ኤደን ያመሩ ሲሆን እዚያ ከሚገኘው ከታጠቀ ወታደራዊ ኃይል ጋር ባለው ውዝግብ ዙሪያም ተወያይተዋል፡፡ እራሱን የደቡብ የለውጥ ካውንስል ብሎ የሚጠራው ቡድን ድጋፍ የሚያገኘው የተባበሩት አረብ ኢምሬት ነው፡፡ ሁለቱም ቡድኖች በሳውዲ መሪነት በኢራን ድጋፍ እያገኘ የሚዋጋውን የሀውቲ አማፂ ቡድን ጋር ላለፉት ዓመታት እየተዋጉ ነበር፡፡
ባለፈው ሳምንት በተሰጠው መግለጫ የሀዲስና ጠቅላይ ሚኒስትር አህመድ ቢን ዳግሀር የደቡብ የለውጥ ካውንስል ብሎ የሚጠራው ቡድን ላይ ጥቃት ለማድረስ አስበዋል በሚል ክስ እንደቀረበባቸው ዘገባው ያትታል፡፡ በዚህ ምክንያት ለተወሰነ ወራት በየመን መንግሥትና የደቡብ የለውጥ ካውንስል ብሎ የሚጠራው ቡድን መካከል ውጥረት ነግሶ ነበር፡፡ ሁኔታው የርስ በርስ ግጭትና ጥቃትን ኢላማ ያደረገ መሆኑንም ዘገባው አስታውቋል፡፡ እነዚህ በቅርቡ የተፈጸሙ ክስተቶች ደግሞ በየመን ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ግጭት ከማባባስ በተጨማሪ የንፁሀን ዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ የአገሪቱን አንድነት አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል ዘገባው ይጠቁማል፡፡
የደቡብ የመን ታሪክ
በደቡባዊ የመን አካባቢ ያለው ስሜትና ሁኔታ ቀደም ሲል ከነበሩ ታሪካዊ ክስተቶች ጋር ተዳምሮ አሁን ድረስ ያለውን ፖለቲካዊ አቀማመጥ ለተለያዩ ችግሮች ዳርጎት ቆይቷል፡፡ እንግሊዝ እአአ ከ1830 እስከ 1967 ድረስ በአረቡ አገራት በቅኝ ግዛት ይዛ የቆየችውና በቀጥታ ያስተዳደረችው ኤደንን ብቻ ነበር፡፡ በወቅቱ እንግሊዝ በኤደን የራሷን አስተዳደር አቋቁማ የንግድና የትምህርት ተቋማትን ማስፋፋቷን ዘገባው አስታውሷል፡፡
ከተማዋም የተለያዩ ባህሎችና ብሔረሰቦችን ያቀፈች ስትሆን በከተማዋ የህንድና የሶማሌ ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡ እአአ በ1967 ላይ እንግሊዝ ከከተማዋ ስትወጣ በቀጥታ በእንግሊዝ ቁጥጥር ስር ወደ ነበሩ ደቡባዊ የመን ተቀላቀለች፡፡ በመጨረሻም የየመን ሶሻል ፓርቲ ሥልጣን ሲይዝ በየመን ስር ሆነች፡፡ እአአ መስከረም 1986 ላይ የመን ሶሻል ፓርቲ በመራው በኤደን ከተማ ውስጥ ደም ያፋሰሰ ግጭት ተከሰተ፡፡ ግጭቱ የሰሜንና የደቡብ የመን መዋሃድ ምክንያትም ሆነ፡፡ መዋሀዱ ግን የኤደንን ፖለቲካዊ እንቅቃሴ እንዲባባስ አድርጎታል፡፡
እአአ ከ1994 ጀምሮ የኤደን ከተማ ኢኮኖሚ እያሽቆለቆለ መሄድና በከተማዋ የሚኖሩ ዜጎች ፖለቲካዊ መብቶቻቸው መጣስ እአአ 2007 ላይ አል ሂራክ አል ጃኖቢ የሚባል ሰላማዊ እንቅስቃሴ መጀመር ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህም እንቅስቃሴ በወቅቱ የየመን ፕሬዚዳንት የነበሩትን አሊ አብዱላሂ ሳላህ በሥልጣን የመቆየት ሁኔታ ተፈታትኖ ነበር፡፡ እአአ 2011 ላይ አብዱላሂ ሳላህ በአገሪቱ በተካሄደው ተቃውሞ ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ አል ሂራክ ቦታውን አግኝቷል፡፡
እአአ መጋቢት 26 ቀን 2015 የሳውዲ መንግሥት የመራው ጦርነት ከመጀመሩ ከሳምንታት በፊት የአል ሂራክ ደጋፊዎች ኤደን ከተማን ከሀውቲዎች ለመታደግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርገው ነበር፡፡ የተባበሩት አረብ ኢምሬት ሳውዲ ከምትደግፋቸው ቡድኖች በተቃራኒ በመቆም ደቡባዊ የመን ከተሰነዘረበት ጥቃት እራሱን እንዲከላከል ድጋፍ አድርጋለች፡፡
በኤደን የተከሰቱ ግጭቶች
የነፃነት ጥያቄ ከሀውቲዎች ከመምጣቱ በፊት ኤደን የተለያዩ የጸጥታ ችግሮች፣ የኢኮኖሚና መሠረታዊ የተባሉ መሠረተ ልማቶች ያልተሟሉበት ከተማ ነበረች፡፡ እስከቅርብ ዓመታትም በሰሜኖቹ ስትደገፍ ቆይታለች፡፡ ከተማዋ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚንቀሳቀስ ነገር ግን ከሙስሊም ወንድማማች ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚጠረጠረው ሃዲ አሊድ ኢስላህ ፓርቲ እንቅስቃሴም አስተናግዳለች፡፡ በተጨማሪ የሳላፊ እንቅስቃሴ ደጋፊ የተባሉ ኢማሞች ባለፉት ወራት በጥይት ተገድለዋል፡፡
እአአ 2017 ሚያዝያ ወር ላይ የፕሬዚዳንት ሃዲ ታማኝ ወታደሮች የኤደን ከተማ አስተዳዳሪን ኤዳሪዎች ዙባዲን በከተማዋ ኤሬፖርት አካባቢ አግተውት እንደነበር ዘገባው ያሳያል፡፡ እአአ ግንቦት 2017 ዙባዲ የደቡብ የለውጥ ካውንስል የሚባል ፓርቲ መመስረቱን አስታወቀ፡፡ ሀዲ እና ቢን ዳግሀር የደቡባዊ ኤደንን የመንግሥታቸው መቀመጫ አድርገዋታል፡፡ እንደዚህም ሆኖ የ አል ዙባዲን እንቅስቃሴ መቆጣጠር አልቻሉም፡፡
አል ዙባዲ በደቡብ የለውጥ ካውንስል ፓርቲ ውስጥ የተቀላቀለ ሲሆን ፓርቲው በተባበሩት አረብ ኢምሬት የመሣሪያና የገንዘብ ድጋፍ ይደረግለታል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኤደን ከተማ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተባባሰ ይገኛል፡፡ የዓለም መንግሥታት በአካባቢው ያለውን ጦርነት በተለይ ከሀውቲ ጋር ያለውን ግጭት ትኩረት የሰጡ ቢሆንም በኤደን አካባቢ ያለውን ውጥረት ለማርገብ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት እየሰራም ነው፡፡
በቅርቡ በተከሰተው ግጭት የሀዲ መንግሥት የሰጠው ምላሽ በደቡባዊ የመን አካባቢ ያለውን ሁኔታ ይለውጠዋል ተብሎ ተገምቷል፡፡ የፕሬዚዳንት ሀዲ ወታደሮች ኤደንን አካባቢን መቆጣጠር በአካባቢው ያለውን ሁኔታ ከመለወጥ በተጨማሪ የመን በቅርቡ ወደ አንድነት ሊመልሳት ይችላል ሲልም ዘገባው አትቷል፡፡
ነገር ግን የኤደን ዕጣ ፈንታ የተባበሩት አረብ ኢሚሬት በምትወስደው እርምጃ ይወሰናል፡፡ አሁን ያለው ጦርነት ከመጀሩ በፊት የተባበሩት አረብ ኢምሬት ከሰሜን የመን ይልቅ ደቡባዊ ክፍሉ ላይ ትኩረት አድርጋ ነበር፡፡ የተባበሩት አረብ ኢምሬት በኤደን አካባቢ በሚገኘው ባብ አል ማንዳብ ወደብ ላይ የወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ፍላጎት እንዳላት ዘገባው ያስረዳል፡፡
ሳውዲ አረቢያ ወዴት ነች?
የሳውዲ መንግሥት ትኩረት አድርጎ የነበረው በደቡባዊ ክፍል በሚገኘው ድንበር አካባቢ ባለው የፀጥታ ሁኔታ ላይና በአካባቢው የሀውቲ ጥቃት ላይ ነበር፡፡ በዚህም የተባበሩት አረብ ኢምሬት ጋር ግልፅ የሆነ ትብብር ባለመኖሩ በደቡባዊ የመን ያልተጠበቀ ግጭት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡
የሳውዲ መንግሥት ለየመን ስደተኞችና ለአገሪቱ የፖለቲካ ዕጣ ፈንታ ኃላፊነት አለባት፡፡ ለዚህም በደቡባዊ የመን ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ መስጠትም ይጠበቅባታል፡፡ አሁን ባለው ግጭት ሳውዲ ፈጣን የሆነ መደምደሚያ ላይ መድረስ እንዳለባትና የየመን ችግር ከስሩ ለመፍታት ከተባበሩት አረብ ኢምሬት ጋር ተስማምታ በአካባቢው በተለይ በኤደን ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር መስራት እንዳለባት ዘገባው ይጠቁማል፡፡
በኤደን አካባቢ ያለውን ፖለቲካዊ ውጥረት ለማርገብ የሳውዲ መንግሥት የደቡብ ለውጥ ካውንስል ፓርቲና ከሀዲ መንግሥት ጋር ድርድር ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ነገር በግን የደቡብ ለውጥ ካውንስል ፓርቲን ማጥቃት ችግሩን ሊያባብሰው እንደሚችል ዘገባው ይጠቅሳል፡፡
ሳውዲ ከላይ ከተቀመጡት አንዱን በመምረጥ በየመን የሚታየውን ችግር መፍታት ይገባታል፡፡ ነገር ግን ሳውዲ የምትወስደው እርምጃ ምን ይሁን ምን በደቡባዊ የመን አካባቢ ሰላምና መረጋጋት ላያመጣ ይችላል የሚል ፍራቻ መፈጠሩን ዘገባው ይጠቁማል፡፡
ሌላው ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ በደቡባዊ የመን አካባቢ ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ኤደን እራሷን ለማስተዳደር ፍላጎት እንዳላት ማሳያዎች መፈጠራቸው ነው፡፡ በቅኝ ግዛት ዘመን ጀምሮ የዘር ሐረጋቸው የሚመዘዘው የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ ሰዎች ድጋሚ እራሳቸውን የማደራጀትና የመተባበር ሁኔታዎች ተስተውለዋል፡፡ በዚህም እንደ ቀድሞ በአንድ መንግሥት የመተዳደር ፍላጎት የላቸውም፡፡
በምሳሌነት ዘገባው ያነሳው፤ በቅርቡ ተገንጥላ እራሷን በማስተዳደር ላይ የምትገኘው ደቡብ ሱዳን የፖለቲካ አለመረጋጋትና በነዋሪዎቹ ላይ የስደትና ሌሎች ጉዳቶች መድረሳቸውን ነው፡፡ ደቡብ ሱዳን ከተገነጠለች ከሰባት ዓመት በኋላ እንኳ ለሌሎች መገንጠል ለሚፈልጉ አገራት ማሳያ እንደሆነች ዘገባው ያትታል፡፡
በአሁን ሰዓት ያሉን አሳማኝ ምክንያቶችን በመጠቀም ኤደን ከተማን ከገባችበት ችግር ማላቀቅ ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ በአሁኑ ጊዜ ያለው ግጭት እየተባባሰ ከሄደ በከተማዋ አዲስ የመብት ጥሰቶችና አለመረጋጋቶች በኤደንና በሌሎች የመን ከተማዎች ላይ እንደሚከሰት ዘገባው ያመለክታል፡፡

መርድ ክፍሉ

Published in ዓለም አቀፍ
Monday, 05 February 2018 16:43

«ሙሰኛው» የታለ?

ያለንበት 21ኛው ክ/ዘመን ዓለማችን ከፍተኛ የእድገት ደረጃ ላይ የደረሰችበት ዘመን መሆኑ በተደጋጋሚ የሚነገር እውነታ ነው፡፡ በአንጻሩ ከእድገቱ ጎን ለጎንም ዓለም በርካታ ተግዳሮቶችንም ታስተናግ ዳለች፤ ሽብርተኝነት፣ የእርስ በርስ ግጭት፣ የኒውክለር የጦር መሣሪያ ስጋት፣ ወዘተ፡፡ ከእነዚህ ስጋቶች ባልተናነሰ ደግሞ ሙስና አንዱ የዘመኑ የሰው ልጅ ተግዳሮት እየሆነ ይገኛል፡፡ በተለይ በማደግ ላይ ባሉ አገራት ሙስና አንዱ የእድገት ፀር እየሆነ ከመጣ ሰነባብቷል፡፡ ያም ሆኖ ግን ሙስናን መዋጋት ቀላል ሥራ አይደለም፡፡ ሙስናን ለመከላከል የሚደረጉ ጥረቶችን አዳጋች ከሚያደርጉ ፈተናዎች ውስጥ አንዱ ስለሙስና ያለን የተለያየ አረዳድ ወይም ግንዛቤ ነው፡፡
በአንድ ወቅት በአንድ መንግሥታዊ ተቋም ዓመታዊ ግምገማ ላይ ተሳታፊ ሆኜ ነበር፡፡ በዚህ ግምገማ ላይ ለሂስና ግለሂስ በተገምጋሚው እንዲነሱ ከተቀመጡ ነጥቦች መካከል ደግሞ አንዱ «ከኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር የፀዳና ኪራይ ሰብሳቢነትንም ለመዋጋት ያለው ቁርጠኝነት» የሚል ነጥብ የያዘ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የግምገማው አካሄድ በቅድሚያ እንደአካል ተቋሙ ያለበት ሁኔታ ይገመገማል፤ ቀጥሎም እያንዳንዱ ተገምጋሚ በቅድሚያ ራሱን የሚያይበትና ቀጥሎም በሌሎች የግምገማው ተሳታፊዎች ሂስ የሚሰጥበት አሠራር ነው ያለው፡፡ በዚህ መሠረት በቅድሚያ ተቋሙ እንደ አካል ሲታይ ኪራይ ሰብሳቢነት መኖሩ ተገለጸ፡፡ የማይናገረው ተቋምም ሙሰኛ መሆኑ ተጠቆመ፡፡ እያንዳንዱ አባልም በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ራሱን እያየና ሌሎች የሚሰጡትንም ሂስ እየተቀበለ ግምገማው ቀጠለ፡፡ አስገራሚው ነገር ወደ ግለሰቦች ሲወርድ አንድም ሰው ኪራይ ሰብሳቢነት ይገልጸኛል አለማለቱ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ኪራይ ሰብሳቢነትን መዋጋት ላይ እጥረት አለብኝ ከማለት ውጪ ኪራይ ሰብሳቢነት ይገልጸኛል ለማለት አልደፈረም፡፡
በርግጥ «እኔ ኪራይ ሰብሳቢ ነኝ» ወይም «የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት በውስጤ አለ» የሚል ሰው ይገኛል የሚል የዋህ አስተሳሰብ የለኝም፡፡ ምክንያቱም ማንም ሰው እንዲህ ዓይነት አስነዋሪ ተግባርን አለብኝ ብሎ ለመቀበል ሰዋዊ ባህሪው ራሱን ይሞግተዋል፡፡ ይህን ለማድረግ ለሌሎች መኖር መጀመርን ወይም ለተቀበለው ኃላፊነት ሙሉ ኃላፊነት ተሰምቶት ቀደም ሲል ለፈጠራቸው ስህተቶች ከልብ የመነጨ ፀፀት አድሮበት ስርነቀል የአስተሳሰብና የኃላፊነት ለውጥ ማምጣት አለበት፡፡ ያም ሆኖ ግን ሌላው ገምጋሚም ቢሆን በተገምጋሚው ላይ ኪራይ ሰብሳቢነት ይገልጸዋል ብሎ ለማንሳት የደፈረ አልነበረም፡፡ ምንም እንኳን እያንዳንዱ የግምገማው ተሳታፊ ተገምጋሚው ሰው ኪራይ ሰብሳቢ መሆኑን ቢያምንም ወይም በተለያዩ አጋጣሚዎች ስለእሱ የሚነገረው ነገር ግለሰቡ ኪራይ ሰብሳቢ ስለመሆኑ ቢያውቅም በቂ ማስረጃ የለኝም ብሎ ስለሚሰጋና በዚህም ምክንያት ፍርሃት ስለሚያድርበት በድፍረት «ኪራይ ሰብሳቢ ነህ/ነሽ» ለማለት አይደፍርም፡፡
ከስብሰባው በኋላ ከራሴ ጋር መሟገት ጀመርኩ፡፡ ለመሆኑ ኪራይ ሰብሳቢነትን ወይም ሙስናን እንዴት ነው መዋጋት የሚቻለው፡፡ በትክክልም ሰው ሲሰርቅ በጠራራ ፀሐይ «እኔ ልሰርቅ ነው» ብሎ ባለመሆኑ ይህንን ችግር ለመዋጋት ምን ያህል አዳጋች ነው የሚለው አስሳሰብ በውስጤ ሰረፀ፡፡ እውነት ነው፤ አልኩ ለራሴ፤ ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት ኪራይ ሰብሳቢው ብቻ ሳይሆን ኪራይ ሰጪውም እኩል ተጠያቂ መሆን አለበት፡፡
አገልግሎት ለማግኘት ወደ አንድ ተቋም የምንሄድ ሁለት ሰዎች ካለን ሁለታችንም እንደ አመጣጣችን መስተናገድ እንዳለንብን መረዳት ይገባናል፡፡ ከዚያ ውጪ ግን «በእጅ የሚሄድ» እና «በእግር የሚሄድ» እየተባለ የአገልግሎት አሰጣጡ የሚለያይ ከሆነ የመልካም አስተዳደር ችግር ያስከትላል፡፡
ስለኪራይ ሰብሳቢነት ወይም በትንሹ ስለሙስና ስናነሳ በሚሊዮን ወይም ከዚያ በላይ የሚቆጠር ገንዘብ የዘረፉ ሰዎችን በአዕምሯችን እንፈልግ ይሆናል፡፡ በርግጥ ይህ ስህተት አይደለም፡፡ በሚሊዮን ወይም በቢሊዮን የሚቆጠሩ ብሮችን ወይም ዶላሮችን የዘረፈ ሁሉ አንጋፋው ኪራይ ሰብሳቢ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ኪራይ ሰብሳቢ ለመሆን ግን ለዚያ ዝርፊያ አመቺ ቦታ ላይ መገኘትን ይጠይቃል፡፡ እንዲህ ዓይነት ኪራይ ሰብሳቢዎች አገርን የሚጎዳ ተግባር ውስጥ መዘፈቃቸው ግልጽ ነው፡፡ መንግሥትም እንዲህ ዓይነት ኪራይ ሰብሳቢዎችን ለመዋጋት ትግል መጀመሩ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ ውጪ በየጉራንጉሩ ያሉትንስ ኪራይ ሰብሳቢዎች በትክክል እንዋጋቸዋለን? እንዴትስ ልንዋጋቸው እንችላለን? ትዝብቴም በዚህ ላይ ያተኩራል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘም አንድ ገጠመኜን ላውጋችሁ፡፡ ጊዜው የ2009ዓ.ም የገና በዓል መዳረሻ ወቅት ነው፡፡ በዓሉን ምክንያት በማድረግና ያለኝን የኢኮኖሚ አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት ለበዓሉ አንድ መካከለኛ በግ ለመግዛት ፈልጌ አዲሱ ገበያ አካባቢ ወደሚገኘው በግ መሸጫ ቦታ አመራሁ፡፡ በቦታው ስደርስም የዕለቱ ገበያ ከወትሮው በተለየ ደመቅ ብሏል፡፡ ያም ሆኖ ግን የበግ ዋጋው ከወትሮው የተለየ አልነበረም፡፡ እናም ዞር ዞር ብዬ የገበያውን ዋጋ ማጥናት ጀመርኩ፡፡ በዕለቱ የገበያ ዋጋ አንድ መካከለኛ በግ በአማካይ እስከ ሁለት ሺህ ብር ድረስ ይሸጣል፡፡ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት እኔም የምፈልገውን አንድ ለዓይን ገብ የሆነ በግ አይቼ ዋጋ ጠየኩ፡፡ ሻጩም የመጀመሪያ ጥሪ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር ነው ሲል ገለጸልኝ፡፡ እኔም በጉን እያገላበጥኩ አይቼ ዋጋ እንዲቀንስልኝ መከራከር ጀመርኩ፡፡ በዚህ መሃል አንድ የመንግሥት ታርጋ የለጠፈ ቶዮታ መኪና መጥቶ ፊት ለፊት ሲቆም ነጋዴው ተመለከተ፡፡ በፍጥነትም ከእኔ ራቅ ብሎ በጎቹን በያዘው ረጅም ቀጭን ዱላ ከፊታቸው መለስ መለስ እያደረገ አጠቃላይ ትኩረቱን ወደ ሰዎቹ አደረገ፡፡ ሰዎቹም በቀጥታ ወደ እሱ መጡ፡፡ እኔም በዚህ መካከል ተረሳሁ፡፡
ነጋዴው ሰዎችን ከዚህ በፊትም ያውቃቸው ኖሮ እየተሽቆጠቆጠ ሰላምታ ከሰጣቸው በኋላ ምን ልስጣችሁ የሚል ጥያቄ አቀረበላቸው፡፡ እነሱም አንድ ጥሩ በግ አምጣልን አሉት፡፡ በዚህ ጊዜ እኔ መርጬ ስከራከርበት የነበረው በግ ለአዲሶቹ ገዢዎች ቀረበ፡፡ እነሱም ዋጋውን ጠየቁ፤ ሦስት ሺህ አምስት መቶ ብር መሆኑም ተነገራቸው፡፡ ጆሮዬን መጠራጠር ጀመርኩ፡፡ በዚህ ደቂቃ ውስጥ አንድ በግ እንዴት አንድ ሺህ ብር ሊጨምር ይችላል ፡፡ ሰዎቹም ብዙ የሚከራከሩ አልነበሩምና በል ጫነው ብለው እጃቸውን ወደኪሳቸው ከተቱ፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ እኔም ልገዛ የነበረውን በግ በአዲሱ ጨረታ ተነጠቅሁ፡፡ የገበያውም ዋጋ በአንድ ጊዜ አሻቀበ፡፡ ጉዳዩ በጣም ስለገረመኝ እነዚህ ሰዎች እነማን እንደሆኑ ለማጣራት ሞከርኩ፡፡ የአንድ መንግሥታዊ ተቋም የሥራ ኃላፊዎች መሆናቸው ተነገረኝ፡፡ እንግዲህ አስቡት እነዚህ ሰዎች ተቀጣሪ ሆነው እንዴት ነው ለሚያወጡት ወጪ ቢያንስ የማያሳስባቸው፡፡ ከጀርባቸው ያልለፉበት የኪራይ ገንዘብ ሊኖር እንደሚችል ታዝቤ (ግን ማረጋገጫ አልነበረኝም) ዝምታን መረጥኩ፡፡
እንግዲህ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ናቸው ገበያውን የሚያዛቡት፡፡ ነጋዴው በአግባቡ እንዳይሰራም በራሳቸው መንገድ ገበያውን የመረበሽ አቅማቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ነጋዴ የማይገባውን ጥቅም ለማግኘት የሚጥር ቢሆንም የእነዚህ ሰዎችም ድርጊት የራሱ አስተዋፅኦ እንዳበረከተ እገምታለሁ፡፡ የሙስና ተግባር ባለዘርፈ ብዙ ድርጊቶች ጥርቅም ችግር ነውና፡፡
በአጠቃላይ ሙስና የአገር ጠንቅ ነው፡፡ በአንድ አገር ላይ ሙስና ከተንሰራፋ ለአገሪቷ እድገት ማነቆ ይሆናል፡፡ ሕዝቦቿም ሰርተው አገርን ለመለወጥ የሚያደርጉት ተነሳሽነት ይቀንሳል፡፡ በሕጋዊ መንገድ ሰርቶ ከማደግ ይልቅ አቋራጭ መንገዶችን መፈለግ ባህል ይሆናል፡፡ ስለዚህ የመልካም አስተዳደር ችግር የአገሪቷ ዋነኛ መገለጫ ይሆናል፡፡ እናም ይህ ክፉ የእድገት ጠላት በመሆኑ ልንዋጋው ግድ ይላል፡፡
ሰሞኑን በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የተከበረውን የጥምቀት በዓልና 30 ኛውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ መሠረት በማድረግ በርካታ የውጭ አገር ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የውጭ አገር ጋዜጠኞች፣ የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የአገራት መሪዎች እንዲሁም ቱሪስቶች የዚሁ አካል ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ደግሞ ለአገራችን ሁለት ዋና ዋና ጠቀሜታዎች ይኖሩታል፡፡ በአንድ በኩል ከእነዚህ የውጭ አገር ዜጎች አገሪቱ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ለኢኮኖሚው የሚኖረው ተደማሪ አቅም ቀላል አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ የውጭ አገር አካላት ስለአገራችን አጠቃላይ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ የሚያገኙዋቸው መረጃዎች እና ከዚህ ጋር ተያይዞ ስለአገራችን የሚያስተላልፉት መረጃ የአገራችንን ገፅታ ለመገንባትም ሆነ ለማበላሸት የራሱ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ በዚህ የተነሳ በየትኛውም ምክንያት ቢሆን የእነዚህ የውጭ አገር ዜጎች በአገራችን በሚኖራቸው ቆይታ የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ጠቃሚ በመሆኑ እኛነታችንን ሊያሳይ የሚችልና ኢትዮጵያውያን የምንታወቅበትን የእንግዳ ተቀባይነት ባህል ይበልጥ አጉልተን ማሳየት ይጠበቅብናል፡፡
ያም ሆኖ ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንዲህ ዓይነት ኢትዮጵያ የምትኮራባቸውን ባህሎቻችንን ሊያጎድፉ የሚችሉ አስነዋሪ ተግባራት አልፎ አልፎ እንደሚስተዋሉ ሰማሁ፡፡ ለአብነትም የውጭ አገር ዜጎች ሲመጡ ከእነዚህ ሰዎች የማይገባንን እላፊ ለማግኘት በምንሰጣቸው አገልግሎቶች ላይ ዋጋ መጨመር አልፎ አልፎም ተጨማሪ ክፍያ (ቲፕ) የመፈለግ አዝማሚያና ሌሎች ያልተለመዱ ተግባራት እየተስተዋሉ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ተግባራት በራሳቸው የኪራይ ሰብሳቢነት ዋነኛ መገለጫዎች ናቸው፡፡ ያውም የአገርን ገፅታ በእጅጉ ሊያበላሹ የሚችሉ ትላልቅ የሙስና መገለጫዎች፡፡
በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የተሰማሩ አንዳንድ አካላት አላግባብ ከትራንስፖርት ታሪፍ በላይ በመጨመር ከፍ ያለ ክፍያ መጠየቅ፣ አንዳንድ ሆቴሎች የውጭ ዜጋ ሲመጣ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ፣ እነዚህን የውጭ አገር ዜጎች በተለያየ መንገድ እንዲያጓጉዙ የተመደቡ የመንግሥት ተሽከርካሪ ሾፌሮች ተጨማሪ ክፍያ (ቲፕ) መጠየቅ እና ሌሎች ያልተገቡ ተግባራት አልፎ አልፎ ይስተዋላሉ፡፡ እነዚህ ተግባራት ደግሞ ተጠቃሚውን አካል ከማማረራቸውም በላይ የውጭ አገር ዜጎች ስለአገራችንና ስለመልካም እንግዳ ተቀባይነታችን የነበራቸውን አወንታዊ እይታ የሚያንሸዋርሩና በሂደትም የአገርን ገጽታ የሚያበላሹ ተግባራት በመሆናቸው ሊታሰብበት ይገባል፡፡
በአገራችን አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት በትንንሽ ደረጃ ላይ የሚታዩ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራት ዋነኛ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እየሆኑ ነው፡፡ ከሕዝብ በተሰበሰበ ግብር የሚከፈለውን ደመወዝ ወደ ጎን በመተው ለሚሰራት እያንዳንዷ አገልግሎት ከግለሰብ ኪስ ጥቂት ብሮችን የሚጠብቅና ጉርሻ ካልተሰጠው ከተቀመጠበት ወንበር የማይነሳ የመንግሥት ተቀጣሪ ሠራተኛ፣ የዶላር ዋጋ ጨምሯል በሚል ከውጭ ምንዛሪ ጋር ምንም ዓይነት ንኪኪ የሌለውን የአገር ውስጥ ምርት ከተጨመረው የዶላር ዋጋ ሦስት እጥፍ ጨምሮ የሚሸጥ ነጋዴ፣ መብራት ጠፋብኝ ስትለው ትንሽ ቲፕ ካልሰጠኸው በወቅቱ በፍጥነት የሚፈለገውን አገልግሎት ለመስጠት እግር የሚጎትት የቴከኒክ ሠራተኛ፣ የመንግሥት ደመወዝ ተጨመረ ሲባል በማግስቱ የቤት ኪራዩን በእጥፍ የሚጨምር የቤት አከራይና የሸቀጣ ሸቀጥ ዋጋ ላይ ጭማሪ የሚያደርግ ነጋዴ፣ ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች ወይም ለሚሸጣቸው ዕቃዎች ተገቢውን ደረሰኝ የማይቆርጥ ነጋዴና ለገዛው ዕቃም ወይም ለተቀበለው አገልግሎት ደረሰኝ የማይጠይቅ ተገልጋይ፣ በትምህርት ቤት በኩረጃ ለማለፍ ዓመቱን ሙሉ ምንም ሳያጠና ቁጭ ብሎ የሚከርምና ፈተና ሲደርስ በኩረጃ ለማለፍ ጎበዙን ወይም ጎበዟን ተማሪ የሚያስጨንቅ ሰነፍ ተማሪ፣ ወዘተ የኪራይ ሰብሳቢነት ዋነኛ መገለጫዎች አይደሉምን? እነዚህ አካላት ዕድሉን ቢያገኙ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከመዝረፍ የሚያግዳቸው ማነው? ኃላፊነቱስ የማነው? እንዲህ ዓይነት ኪራይ ሰብሳቢነት በየቦታው አለ፡፡ ምንም ተጨማሪ እሴት ባልጨመረበት ከልፋቱ ውጪ የማይገባውን ለመዝረፍ ሌት ተቀን የሚተጋ፡፡
በተለይ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንደመሆኗ ለሁሉም አፍሪካውያን የመኖሪያ ቤታቸው ያህል ነፃነትና የኔነት ስሜት እንዲሰማቸው ማድረግ ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው፡፡ አላግባብ የውጭ አገር ዜጎችን አገኘን ብለን ያልተገቡ የዋጋ ጭማሪዎችን የምናደርግም ሆነ የውጭ ዜጋ ስናይ ሳንቲም የሚጥል ይመስል ከኋላቸው የምንከተል ካለን ግን ቆም ብለን ስለክብራችንና ኢትዮጵያዊነታችን ልናስብ ይገባል፡፡
በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት እንድንሰጥ የተቀመጥን የመንግሥት ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎችም ኪራይ ሰብሳቢነትን በርቀት አሻግረን ከመመልከት ይልቅ አቅርቦ በሚያሳይ መነፅር ከቅርባችን ያለውን ወይም በላያችን ላይ የተለጠፈውን ኪራይ ሰብሳቢ አስተሳ ሰባችንን እንየው፡፡ ቆም ብለን ራሳችንን ካልፈተሽነው ኪራይ ሰብሳቢነት «መንፈስ» ነው፡፡ ቶሎ ላይታየን ይችላል፡፡ ዛሬ ቀኑን ሙሉ ምን ሰራሁ? የምሰጠውንስ አገልግሎት ምን ያህል በቅንነትና በታማኝነት ሰራሁ? ከእኔ አገልግሎት የሚፈልጉ ተገልጋዮች በምሰጠው አገልግሎት ምን ያህል ረክተው ተመለሱ? የሚፈለገውን አገልግሎትስ ምን ያህል በፍጥነት መስጠት ችያለሁ? ለሚሉ ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ ለመስጠት ራሳችንን የምንጠይቅ ከሆነ ያለጥርጥር ግለሂሱን ከወዲሁ ጨርሰናል ማለት ነው፡፡ ያኔ «ኪራይ ሰብሳቢነት አይገልፀኝም» ብንልም ተገቢ ይሆናል፡፡ በትንሹ ያልታመነ ከትልቁ ቦታ ቢገኝም ሊታመን አይችልምና፡፡

ውቤ ማሩ

Published in አጀንዳ

ሰሞኑን የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የስድስት ወር ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ነበር፡፡ በሪፖርቱም ባለፉት ስድስት ወራት የሰበሰበው ገቢ ከእቅዱ በታች መሆኑን አመልክቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ የግብር ከፋዩ የሕግ ተገዢነት ማነስ የችግሩ ምንጭ እንደሆነ በሪፖርቱ አስፍሯል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም በተለይ አንዳንድ ግብር ከፋዮች ገቢን አሳውቆ ከመክፈል ይልቅ በተለያየ መንገድ ግብር የማይከፍሉበትን ወይም አነስተኛ ግብር የሚከፍሉበትን መንገድ የሚፈልጉ መሆናቸውን አብራርቷል፡፡ ለተሸጡ ዕቃዎች ተገቢውን ደረሰኝ አለመስጠት፣ የቫት ደረሰኝ ሳይቆርጡ መሸጥ እና መግዛት፣ የሂሳብ መዝገቦችን በትክክል አለመያዝ፣ በሕገወጥ መንገድ ቀረጥ ሳይከፈልባቸው ዕቃዎችን ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት እና የመሳሰሉ ተግባራት ከግብር ጋር ተያይዞ ከሚከሰቱ ችግሮች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ግብር የሀገር መሠረት ነው፡፡ ግብር ከሌለ መንግሥት አይኖርም፡፡ መንግሥት ከሌለ ደግሞ ሀገር አይኖርም፡፡ እናም ለግብር ያለን አተያይ ከመነሻው ሊታረም ይገባል፡፡ ግብር ማለት ሰዎች በተለያየ መንገድ ሰርተው ከሚያገኙት ገቢ ላይ የሚከፈልና መልሶ ለጋራ ልማት የሚውል የጋራ ሀብት ነው፡፡ ስለዚህ ግብር ስንከፍል ከምናገኘው ገቢ ላይ የምናወጣው ወይም በኪሳራ የምንመዘግበው መሆን የለበትም፡፡ ይልቁንም ለምንሰራው ሥራ ቅልጥፍና የሚያግዝ ድጋፍ ሰጪ አቅም መሆኑን መገንዘብና በፍላጎት ላይ ተመስርተን በኃላፊነት መንፈስ መክፈል እንዳለብን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ሥራዎች የሚከናወኑት ከግብር በሚሰበሰብ ገቢ ነውና፡፡
አሁን ያለውን የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታም ስንመለከት የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መሠረታዊ የሕዝብ አጀንዳዎች ሆነው የወጡበት ጊዜ ነው፡፡ ለዘመናት በውድቀት ውስጥ የቆየው የሀገራችን ኢኮኖሚ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት መነቃቃትን በማሳየት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ኢኮኖሚ መነቃቃት ደግሞ ለዘመናት የተከማቸውን የሕዝቦቿን የልማት ጥያቄ በአግባቡ እንዲመልስ ለማድረግ አሁን እየሄደ ካለው ፍጥነትም የበለጠ መፍጠንን ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ኃይል የሚሰበስበው ግብር ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከሩብ ምዕተ ዓመት በፊት የነበረችበትን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት ምንም ዓይነት የመሠረተ ልማት እንቅስቃሴ ያልነበረባት በመሆኗ በባለሀብቱ ተመራጭ አገር አልነበረችም፡፡ በተለይ ለልማት ዋነኛ ግብዓት የሆኑት የመንገድ፣ የኃይል አቅርቦት፣ የቴሌኮሙኒኬሽንና የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶች የነበሩበት ደረጃ ገና በጅምር ላይ የነበረ በመሆኑ እነዚህን ማስፋፋት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም መንግሥት በእነዚህ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡
ከዚህም ጎን ለጎን በሀገራችን ለዘመናት ስር ሰዶ ለቆየው ችግር አንዱ የተማረ የሰው ኃይል በሚፈለገው ደረጃ አለመኖር እንደሆነም ይታወቃል፡፡ ይህን ስር የሰደደ ችግር ለመፍታት ደግሞ መንግሥት ለትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በዘርፉ እመርታ ለማምጣት እየሰራ ይገኛል፡፡ ትምህርት ደግሞ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይን የሚጠይቅ የማህበራዊ ዘርፍ ነው፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታም 30 ሚሊዮን የሚጠጋ የሀገራችን ወጣት የኅብረተሰብ ክፍል በትምህርት ላይ በመሆኑ ይህንን ኃይል በአግባቡ ውጤታማ ለማድረግ ከፍተኛ የገንዘብ አቅምን ይጠይቃል፡፡
በጤና ዘርፍም ቢሆን የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ በከፍተኛ ችግር ውስጥ የወደቀበት ሁኔታ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በተለይ በገጠር የነበረው የጤና ተቋማት ሁኔታ አነስተኛና ተደራሽ ያልነበረ በመሆኑ በርካታ ዜጎች በህክምና እጦት ሕይወታቸው ሲያልፍ ማየት የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ በገጠርም እናቶች ያለ ጤና ባለሙያ ድጋፍ በየቤቱ የሚወልዱበትና ለችግር የሚጋለጡበት ሁኔታ የአብዛኛው የሀገራችን ክፍል መገለጫ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይህንን ነባራዊ ሁኔታ መቀልበስ ደግሞ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡ መንግሥትም የጤና ተቋማትን የማስፋፋት፣ የጤና ባለሙያዎችን አቅም የማጎልበት እና መከላከልን መሠረት ያደረገ የጤና ፖሊሲን በመተግበር የኅብረተሰቡን የጤና ሁኔታ የማሻሻል ሥራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡
በሌላ በኩል መንግሥት ሰላምን የማስከበር ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ እያንዳንዳችን በሰላም ወጥተን በሰላም የምንገባውም ሆነ ልጆቻችንን ወደ ትምህርት ቤት የምንልከው ሰላም በመኖሩ ነው፡፡ ይህም እውን የሚሆነው መንግሥት እነዚህን ሥራዎች በአግባቡ ለማከናወን የሚያስችለውን ግብር በአግባቡ መሰብሰብ ሲችል ብቻ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡
እነዚህና ሌሎች በመንግሥት የሚከናወኑ ዘርፈብዙ ተግባራት ዋነኛ መሠረታቸው ግብር ነው፡፡ ሥራዎቹ ደግሞ የአንድ ሰው ወይም የተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል ሀብቶች አይደሉም፡፡ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የጋራ ንብረቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህና መሰል የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች በአግባቡ እንዲቀጥሉና ኅብረተሰቡም ከእነዚህ ትሩፋቶች ተጠቃሚ እንዲሆን የሚጠበቅብንን ግብር በወቅቱ እና በአግባቡ መክፈል ከእያንዳንዱ የግብር ከፋይ የሚጠበቅ ግዴታ ነው፡፡
በተለይ በተለያዩ የንግድ ሥራ ላይ የተሰማራን የኅብረተሰብ ክፍሎች የግብር መክፈያ ወቅት ደርሶ ግብር እንድንከፍል ስንጠየቅ ግብርን ለመደበቅ ከምንሯሯጥ ከወዲሁ የግብር መክፈያ ጊዜው ከመድረሱ በፊት ከፊታችን ግብር እንደሚጠብቀን አውቀን ዝግጅት ማድረግ ይገባናል፡፡ በሌላ በኩል ግብርን መደበቅም ሆነ የሚጠበቅብንን ኃላፊነት አለመወጣት ተጠያቂ እንደሚያደርግ አውቀን ኃላፊነታችንን ለመወጣት ዝግጁ መሆን ከሁሉም ግብር ከፋይ ይጠበቃል፡፡

 

Published in ርዕሰ አንቀፅ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።