Items filtered by date: Tuesday, 06 February 2018

ይህን አርቲክልባለፈው ሳምንት ጥር 22 ቀን 2010 ይዘን መውጣታችን ይታወሳል። አርቲክሉ በገጽ ዝግጅት ወቅት በተፈጠረ ስህተት ይዞት መውጣት የነበረበት መረጃ ተቆርጦ ከመቅረቱም በተጨማሪ አላስፈላጊ መረጃ ተካቶበትም ነበር። አዲስ ዘመን ለተፈጠረው ስህተት አንባቢያንን ይቅርታ እየጠየቀ በዛሬው አትማችን አርቲክሉን ሙሉ ለሙሉ ይዘን መውጣታችንን እንገልጻለን፡:
በስፖርቱ ዓለም ማናጀሮች «የአብረን እንሥራ» ጥያቄ የሚያቀርቡ የስፖርት ኤጀንት ድርጅት ባለቤትና ተወካዮች፤አሊያም ሠራተኞች ናቸው። ዋነኛ ተግባራቸው ደግሞ የተለያዩ ውድድሮች ላይ ውጤታማ ናቸው የሚሏቸውን ስፖርተኞች መምረጥና የጥቅም ውል መግባት ነው። ማናጀሮች በዓለም ላይ የታወቁ ደላሎች ናቸው።የስፖርት ዓይነቶችን አይመርጡም።በተለይ ከእግር ኳሱና አትሌቲክስ ጀርባ ሁሌም ስማቸው አለ።
አትሌቲክሱን ብንመለከት አንድ ማናጀር በአትሌቱ ከተወከለ በኋላ አይሮጥለትም እንጂ በርካታ ተግባራትን ያከናውናል።በተለያዩ የዓለም አገራት የሚደረጉ ውድድሮችን ከሚያዘጋጁ አዘጋጆች (ባለቤቶች) ጋር ቀጥታ ግንኙነት በማድረግ ለአትሌቶች ውድድር ያመጣል። አትሌቶችን ይልካል። ውድድሮችን ያዘጋጃል፤ያማክራል፤ ይቆጣጠራል።
በማንኛውም ጥቅማ ጥቅም ዙሪያ ያለ አትሌቱ ጣልቃ ገብነት ይደራደራል። አትሌቱን በተመለከተ በማንኛውም ሰነድ ላይ ወክሎ ይዋዋላል። ይፈራረማል። ገንዘቡን ይቀበላል።በዚህ ተግባራችንም በብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ደንብ መሰረት ከአትሌቶች15 በመቶ ኮሚሽን ይቀበላሉ።
ማንኛውም ግለሰብ ማናጀር ለመሆን ፈቃድ አውጥቶ ህጋዊ ሆኖ መመዘገብና የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማህበርን (አይደብልኤፍ) F መስፈርት ማሟላት የግድ ይለዋል።አንድ ማናጀር አትሌቶችን ከተከለከሉ አበረታች መድኃኒቶች የመጠበቅ ፤አትሌቶቹ ከሀገር ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ ጤንነታቸውንና ደህንነታቸውን የመከታተል፤ አትሌቱን ወክሎ የሚያደርጋቸው ውሎች አትሌቱ አውቆትና አምኖበት እንዲፈጸሙ የማድረግ ግዴታም አለበት።
ከዚህ በተጓዳኝ፤ለአትሌቱ የሚሰጡ ክፍያዎችና ወጪዎችን ከውድድሩ በፊት የማሳወቅ እንዲሁም ለአትሌቱ የሚደረጉ ክፍያዎችን በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ የመክፈል፤አትሌቱን ገንዘብ ከማጭበርበር መቆጠብና ትክክለኛውን የሽልማት መጠን ማሳወቅ ግድ ይለዋል።
አትሌቲክስ ሲነሳ ስማቸው ቀድሞ ከሚጠቀስ አገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት የምትጠራውና የበርካታ ስመጥር አትሌቶች መፍለቂያ መገኛ በሆነችው ኢትዮጵያም የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ማናጀሮች ከታዳጊ ጀምሮ እስከ ስመጥር አትሌቶች ድረስ ስማቸውን አቆራኝተዋል።
በተለያዩ ጊዜያት እንደሚሰማው ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በአትሌቶች እና በማናጀሮች መካከል ያለ ቁርኝት በርካታ ክፍተቶችና ከፍተኛ ጭቅጭቅ ያለበትና ባለመግባባትና በአልቃሽና አስለቃሽ ትዕይንት የታጀበ ነው። በተለይ መብት በእጅጉ ይጣሳል።
ውሎች በአግባቡ አይፈፀሙም። በተለይ አብሮ ለመስራት ግልፅነት ቢያስፈልግም አትሌቱ እና ማናጀሩ የሚፈራረሙበት የውል ሰነድ በጋራ ስምምነት የሚዘጋጅ አይደለም።አትሌቶች በማያውቁት ቋንቋ ተሰንዶ የሚቀርብ ነው።አትሌቶቹ የቀረበላቸውን ውል ሲፈርሙም ይተርጎምልን የሚል ጥያቄን አያነሱም።ያለ አማካሪ በግላቸው የቀረበላቸውን ይፈርማሉ።ይዋዋላሉ።
አብረን እንስራ የሚለው ውል ሲዋዋል ጠበቃ አሊያም ህግ የሚያውቅ ሰው አያስከትሉም።እርዱኝ ብለውም አያማክሩም።ወደ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም አይሄዱም። ባለመብት መሆናቸውን አያውቁም። ውላቸውን ቀድመው አይጠየቁም።ያለ ምስክር የፈረመበትን ኮፒ እንኳን አይቀበሉም።የውሉ ዋና ቅጂ ለማን እንደሚሰጥ እንኳ በቅጡ አያውቅም። በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚፈረመው ውል እምነትን መሰረት ያደረገ ብቻ ነው።ይህ ሲሆንም ማናጀሮቹ አትሌቶቹን እንደፈለጉ ለማድረግ አይቸገሩም።በዚህም ምክንያት በርካታ አትሌቶች ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም አጥተዋል።አልቅሰዋል። አብዛኞቹ ሰሚ ቢያጡም ክስ መስርተዋል።
ይህ ግን በተለይ ህጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸውና ወኪሎች ነን በሚል የተሰማሩትን እንጂ ሁሉንም ማናጀሮች የሚወክል አይደለም።በሙያቸው በአግባቡ የሚሰሩና ለበርካታ አትሌቶች ጥቅም ማግኘት እንዲሁም ዝና መጎናጸፍ ተጠቃሽ የሆኑም ጥቂት እንዳልሆኑም እርግጥ ነው።
ይሁንና በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ውድድሮች መበራከታቸውን ተከትሎ በአገራችን የአትሌቶችም ይሆን የማናጀሮች ቁጥር በእጅጉ በመጨመሩ ጉዳዩ ይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የሚያሳስቡ ብቅ ብቅ እያሉ ናቸው፡፡ይህን ሃሳብ ከሚጋሩት መካከል አትሌት ጥላሁን ኃይሌ አንዱ ነው።
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የአትሌቶችም ይሆን የማናጀሮች ቁጥር በእጅጉ በመጨመሩ የሁለቱ አካላት የአብረን እንስራ ትስስር መጎልበቱን የሚገልፀው አትሌቱ ጥላሁን፤ በዚያው መጠን በመካከላቸው ያለው እሰጣ ገባም መጨመሩንና ህጋዊ ያልሆኑ ማናጀሮች መበራከታቸውን ይገልፃል።ጉዳዩ ትኩረት ካልተሰጠው የችግሩ ሰለባ አትሌቶች ቁጥር እንደሚያሻቅብ ይጠቁማል።
እንደ አትሌት ጥላሁን ገለፃ፤ከታዋቂ አትሌቶች ይልቅ ታዳጊ አትሌቶች የዚህ ችግር ዋነኛ ሰለባ ሆነዋል። ታዋቂዎቹ አትሌቶች ውጤታማ ስለሆኑ ህጋዊና ጥሩ ማናጀሮችን አማርጠው ይይዛሉ።ታዳጊና አዳዲስ አትሌቶች በአንፃሩ ውድድሮችን የማግኘትና የማሸነፍ ፍላጎታቸው ከፍተኛ በመሆኑ እንዲሁም ውጤትና የተሻለ ስም ስለሚመኙ በቀላሉ ለመታለል ቅርብ ናቸው።
አብዛኞቹ የችግሩ ሰለባዎችም መብታቸውን እንኳን በቅጡ የማያውቁ በመሆናቸው የቀረበላቸው ውል የልፋታቸውን ያህል አለመሆኑን እያመኑም ይፈርማሉ።በዚህም ምክንያት በርካታ አትሌቶች በማናጀሮቻቸው ይጭበርበራሉ።ይጎዳሉ።በተለይ ሴት አትሌቶች ፆታዊ ጥቃትና ጫና ጭምር ሊደርስባቸውም ይችላል።
«በአሁኑ ወቅት በግል ተፃፅፈው የሚሄዱ አትሌቶች ቁጥር በእጅጉ ጨምሯል፤የዚህን ያህል ችግሩም እያደር ተባብሷል፤የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዚህ የአትሌቶችና የማናጀሮች እሰጣ አገባ በእጅጉ ተሰላችቷል» የሚለው አትሌት ጥላሁን፤በተደጋጋሚ ለፌዴሬሽኑ ክስ የሚያቀርቡ አትሌቶችና ክሳቸውን በቅጡ ማቅረብ አቅም አጥተው ቤታቸው የተቀመጡ አትሌቶች በርካታ መሆናቸውን ይጠቁማል ።
አትሌቶቹ ከዚህ ውሳኔ የሚደርሱት በክለብ ቢታቀፉም እንኳን የሚከፈላቸው ገንዘብ አነስተኛ በመሆኑና የእለት ውጪያቸውን ለመሸፈን ብሎም ኑሯቸውን ለማሸነፍ ሲሉ መሆኑን የሚገልፀው አትሌቱ፤ችግሩን ለማስወገድ መፍትሄው ላይ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ያስገነዝባል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የአትሌቶች ማህበር ሥራ አስፈፃሚ አባል አትሌት ፋንቱ ሚጌሶም የአትሌቱን አስተያየት ትጋራለች፡፡ አትሌት ፋንቱ ቀደም ባሉት ዓመታት ከነበረው ጋር ሲነፃጸር የአትሌቶቹም ይሆን የማናጀሮች ቁጥር በእጅጉ መጨመሩን ፣የሁለቱ አካላት የአብሮነት ሂደት ግን የግል ጥቅምን ብቻ በሚያሳድዱ ማናጀሮች መበራከት ሳቢያ አትሌቶች በጣም እየተበዘበዙ መሆናቸውን ትገልጻለች፡፡
እንደ አትሌቷ ገለጻ፤ማናጀሮች ወደ አንድ አገር የሚመጡት የግል ጥቅማቸውን ታሳቢ በማድረግ ነው። ብዙውን ጊዜ አሻጥር እንደሚሰሩም ግልፅ ነው።ኩባንያዎች ጋር ሲደራደሩ መቶ አሊያም ሃምሳ ሺ ዶላር ሊነጋገሩ ይችላሉ።ከአትሌቶቹ ጋር የሚፈራሩበት ይህን የሚገልጽ አይደለም፡፡ ለአትሌቶቹ በሚሰጡት የውል ሰነድ ላይ የሚያሰፍሩት ግን ከ10 ሺ ዶላር አይበልጥም።
ሁሉም ውል በእንግሊዘኛ የሚሰናዳ ነው። አትሌቶቹ ውሉን ከመፈረማቸው በፊት በአግባቡ አይረዱትም።ውሉንም ረጋ ብለው በአግባቡ እንዲገመግሙትም አይደረግም ፡፡ ማናጀሮቹ በአፋጣኝ እንዲፈርሙ ያስገድዷቸዋል።እናም በማያውቁት ውል ላይ ይፈርማሉ።
መሰል የማጭበርበር ወንጀል ሲፈፀም አትሌቶቹን ወግኖ የሚከራከርና ጉዳዩን የሚከታተል ተቋምም ሆነ ግለሰብ አለመኖሩን የምትገልፀው አትሌቷ፤ በዚህም ምክንያት አትሌቶች ላባቸውን አንጠፍጥፈው ያፈሩትን ገንዘብ እንዳያገኙ ይደረጋል፤ የድካማቸውን ያህል ጥቅም አያገኙም»ትላለች።
እንደ 800 መቶ ሜትር ሩጫ ኮከቧ አትሌት ፋንቱ ሚጌሶ ገለፃ፤ይህ ችግር ትኩረት እንዲሰጠው አትሌቶች በማህበር ብዙ ጥራት ተደርጓል።አሁን ቀደም ሲል ከነበረው የተሻሉ ሁኔታዎች ቢኖሩም ችግሩ ግን አልተወገደም።በዚህ ጉዳይ የአገሪቱ መልካም ገፅታ እየደበዘዘና እየጠፋ ነው።
በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት እጁን እንዲያስገባም አትሌቷ ትጠይቃለች፡፡ «የኢትዮጵያ አትሌቲክ ፌዴሬሽን ይህን ጉዳይ መከታተል አለበት፤ አትሌቶችም ውል ከመፈፀማቸው በፊት በሚያውቁት ቋንቋ ማስተርጎምና ፌዴሬሽኑም የአትሌቶችም ግንዛቤ ማጎልበት ይኖርበታል ›› ትላለች ።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴም ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማድረግ፤አትሌቶችን ለማዘጋጀት እንዲሁም ለማብቃት የማናጀሮቹ መኖር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ይገልፃል።
ይሁንና «ውጭ ወጥተው የሚወዳደሩ አትሌቶች ብዙ ጊዜ ለችግር እየተጋለጡና በተለይ እውቅና የሌላቸው ማናጀሮች እኛ በማናውቀው መንገድ አትሌቶችን ለውድድር ወደ ውጭ ሀገር በተለይም ወደ ቻይና እየላኩ አትሌቶቹም በእጅጉ ጉዳት እየደረሰባቸው ነው» ይላል።
ይህን የአትሌቶችን ጉዳትና በአትሌቶች እና በማናጀሮች መካከል ያሉ አለመግባባት ለማስቆም ደግሞ፤ህጋዊ የሆኑና የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማህበር (አይ ኤኤ ኤፍ) ፈቃድ ያላቸውን 21ማናጀሮች ስም ዝርዝር ይፋ ማድረጉን የገለፀው አትሌት ኃይሌ፤እነዚህ ማናጀሮችም በስማቸው ገናና በምግባራቸውም መልካም የተባሉ መሆናቸውን አስታውቋል።
አትሌቶችም በህገ ወጥ መንገድ ከመንቀሳቀስ በመታቀብ ጉዳያቸውን ወደ ፌዴሬሽኑ ማምጣት አለባቸው ያለው ፕሬዚዳንቱ እውቅና ተሰጥቷቸው ፍቃድ ባገኙ ማናጀሮች አማካኝነት ብቻ እንዲገለገ ሉም ጥሪውን አስተላልፏል፡፡ ከፌዴሬሽኑ እውቅና ውጪ በውጭ ሀገራት ውድድር ላይ በደል የደረሰበትና ተወዳድሮ ገንዘቡን የተቀማ ኃላፊነቱን ራሱ ይወስዳል»ነው ያለው።
እንደ አትሌት ኃይሌ ገለፃ፤ማንኛውም ግለሰብ ማናጀር ለመሆን ፈቃድ አውጥቶ ህጋዊ ሆኖ መመዘገብና የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መስፈርቱን ማሟላት የግድ ይለዋል።ብሄራዊ ፌዴሬሽኑም ዓለምአቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዋቢ ባደረገ መልኩ የማናጀርነትን መስፈርት፤መብትና ግዴታ በህጉ አስቀምጧል።
ፌዴሬሽኑ በዚህ መሰረት የተመዘገቡትን 21ማናጀሮች የመቆጣጠር ተግባር ይፈፅማል።እነዚህ የአትሌት ወኪሎችና ማናጀሮች ህጋዊ መንገዶችን ተከትለው የማይሰሩ ከሆነም እውቅና ከመንጠቅ ባሻገር በወንጀል የሚጠይቃቸው ይሆናል።
‹‹ፌዴሬሽኑ የአገር ውስጥ ማናጀሮችን ለማበረታታት ፈቃድ የመስጠት የድጋፍ ሥራዎች ሲሰራ ቢቆይም ይህን ተግባር ለሌላ ህገ ወጥ ዓላማ ሲጠቀሙ በመታየታቸው አዋጭ አልሆነም ያሉት»ፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ዱቤ ጅሎ፤ፌዴሬሽኑ ለአገር ውስጥ ማናጀሮች ፈቃድና እውቅና መስጠት ማቆሙንም አስረድተዋል።
በርካታ ግለሰቦች ከ50 እና 60 በላይ የሚሆኑ አትሌቶችን ወደ ቻይና እየላኩ መሆኑን የሚገልፁት አቶ ዱቤ፤ይህ ችግር አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱም፤ ፌዴሬሽኑ በከፍተኛ ሁኔታ ቁጥጥር አድርጎ ለቻይና ኤምባሲ እና ለሀገሪቱ አትሌቲክስ ማህበር፤ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ደብዳቤ መፃፉንም አብራርተዋል።
አትሌቶች በህገ ወጥ መንገድ ከመንቀሳቀስ ጉዳያቸውን ወደ ፌዴሬሽኑ ማምጣት እንዳለባቸው እውቅና ተሰጥቷቸው ፍቃድ ባገኙ ማናጀሮች አማካኝነት ብቻ እንዲገለገሉም ጥሪውን ያስተላለፉት አቶ ዱቤ ከፌዴሬሽኑ እውቅና ውጪ ለውድድር የሚደረጉ ጉዞዎች ህገወጥ መሆናቸውንና ኃላፊነቱም የአትሌቶቹ እንደሚሆን ነው ያስታወቁት።

ታምራት ተስፋዬ

Published in ስፖርት

በ2020 የአፍሪካ አገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) አስተናጋጅ ሆና የተመረጠችው ኢትዮጵያ አዘጋጅነቷን የሚያበስር የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አርማ ተረከበች።
አገሪቱ አርማውን የተረከበችው በሞሮኮ አዘጋጅነት የተካሄደው 5 ኛው የአፍሪካ አገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) ከትናንት በስቲያ በካዛብላንካው መሃመድ አምስተኛ ስታዲየም በአዘጋጇ አገር ሞሮኮ አሸናፊነት በተጠናቀቀበት ዕለት ነው፡፡
ከፍፃሜ ጨዋታው በኋላም የካፍ ፕሬዚዳንት አህመድ አህመድ ቀጣይ አዘጋጅ አገር ኢትዮጵያ እንደምትሆን ጠቅሰው፤ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ አገሪቱ አዘጋጅነቷን የሚያበስር የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አርማን አስረክበዋል።በሥነ ሥርዓቱ ላይ ለመገኘት ፕሬዚዳንት ጁነዲን ባሻ እና ጊዜያዊው ዋና ጸሐፊ ሰለሞን ገብረስላሴ መገኘታቸውን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ጁነዲን ባሻ ኦፊሻል ማህበራዊ ድረ ገጽ የተገኘ መረጃ አመልክቷል፡፡
ካፍ ኢትዮጵያን አዘጋጅ ሆና የተመረጠችው በኢሳ ሃይቱ የስልጣን ዘመን ሲሆን፣ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥም በሚቋቋም ቡድን አማካኝነት የካፍ ኢንስፔክሽን ቡድን በ2018 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ውስጥ ኢትዮጵያ ውድድሩን ለማስተናገድ እያደረገች ያለችውን ዝግጅት ይገመግማል ።
ቡድኑ አገሪቱ ውስጥ ያሉት ስታዲየሞች ጥራት እና ለውድድሩ በጊዜው የመድረስ ዕድላቸውን መፈተሽ የመጀመሪያው ሥራው ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች ስታዲየሞችን በመገንባት ላይ ብትገኝም፤ በታሰበላቸው ጊዜ ያለመጠናቀቅ ችግር በሰፊው ይስተዋልባቸዋል፡፡ በባህርዳር፣ ሃዋሳ እና መቀሌ እየተገነቡ ያሉት ስታዲየሞች ባይጠናቀቁም ከወዲሁ ጨዋታዎችን በማስተናገድ ላይ ይገኛሉ፡፡ የባህርዳር እና ሃዋሳ ስታዲየሞች የኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን ማስተናገድም ችለዋል፡፡
ከስታዲየሞች ባሻገር የትራንስፖርት፣ የሆቴል አቅርቦትም ከሚፈተሹ ሌሎች አንኳር ጉዳዮች መካከል የሚመደቡ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በ2007 የሴካፋ ውድድርን ከማስተናገዷ በቀር በአህጉሪቱ ትልቅ ውድድር ካስተናገደች 17 ዓመት አልፏታል፡፡

ዳንኤል ዘነበ 

Published in ስፖርት
Tuesday, 06 February 2018 17:23

ጣፋጭ እና መዘዙ

ጣፋጭ ምግቦችን በተለይም ለልጆች አትስጡ ይባላል። ምክንያቱ የተለያየና ብዙ ቢሆንም ዋናውና መሰረታዊው ግን በጥርሶቻቸው ላይ የሚያደርሰው ዘለቄታዊ ጉዳት ነው። ሆኖም ልጆችና ጣፋጭን መለያየት እንደሚታሰበው ቀላል አይደለም፡፡ የተፈራው የጥርስ በሽታም ብዙዎችን ሲያሰቃይ ስንመለከት ማየቱ ያስቸግራል።
የታሸጉ ምግቦችና መጠጦች እንኳን ህጻናት አዋቂዎችም ማዘውተራቸው ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል።ለዚህ አባባላችን ጥሩ ማሳያው የ32 ዓመቱ አየርላንዳዊ የደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት ነው።
ዘ ኢንዲፔንደንት የተባለው ድረ ገጽ እንደዘገበው የሶስት ልጆች አባት የሆነው ሚካኤል ሻሪዳን ባደረበት የጣፋጭ ምግቦችና የታሸጉ መጠጦች ሱስ ምክንያት በተፈጥሮ ያገኛቸውን ጥርሶቹን ሙሉ በሙሉ በሚያስገርምና በሚያሳዝን መልኩ ለጉዳት ተዳርገዋል ።
በቀን እስከ 6 ሌትር ጣፋጭ መጠጦችን የሚጠጣው ይህ ሰው በአሁኑ ወቅት ጥርሶቹ ከመጎዳታቸው ባሻገር ከፍተኛ በሆነ የራስ ምታት ይሰቃያል፡፡ በሌላ በኩልም እንደልቡ መናገርም ሆነ መሳቅ ባለመቻሉ በልጆቹ እንዲሁም በቤተሰቡ ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ጫናን እንዳሳደረበት ዘገባው ገልጿል።
«ብዙ ጊዜ የማፈርና ምቾት ያለመሰማት ያጋጥመኛል፤ ሳወራም ሆነ ስስቅ ጥርሶቼ እንዳይታዩ ከፍተኛ ጥንቃቄ አደርጋለሁ። የምናገረው ለሰዎች አይሰማም ፤ምክንያቱም አፌን ከፍቼ ማውራት አልፈልግምና›› ሲል ገልጿል።
የገና በዓል በመጣ ቁጥር ሌሎች ሰዎች ሲደሰቱና ፊታቸው በፈገግታ ሲደምቅና እየሳቁ የተለያዩ ፎተግራፎችን ሲነሱ እኔ ግን በከፍተኛ ድብርት ውስጥ ከመውደቄም ባሻገር እንደነሱ በፈገግታ ተሞልቼ ፎቶግራፎችን መነሳት አልችልም » በማለት የጥርሱ ጉዳይ ተደራራቢ ችግር እንደፈጠረበት ይናገራል።
ሻርደን ንግግሩን በመቀጠል በለስላሳ መጠጦች ሱስ ውስጥ በነበረበት ወቅት ጠዋት ከመኝታዬ ተነስቼ ከፍሪጅ የወጣ ቀዝቃዛ ለስላሳ አልያም ሌላ ጣፋጭ ጁስ መጠጣት ካልቻልኩ እራሴን በከፍተኛ ሁኔታ ያመኝ ነበር፤ምናልባት ሱሱ የተለመደ መስሎኝ እራሴን መግታት አለመቻሌ አሁን ላለሁበት ከፍተኛ ችግርና ስቃይ ዳርጎኛል ይላል ፡፡
በአሁኑ ወቅትም 120 ፓውንድ ከፍሎ 27 ጥርሶቹን ለማስወገድ ተዘጋጅቷል፡፡ በዚህም እጅግ በመደሰቱ « ከአሁን በኋላ ያለምንም መሳቀቅ መስታወት ፊት መቆም ብሎም ስቄ ፎቶ መነሳት እችላለሁ፣ ይህንን ላደረጉልኝ የጥርስ ሀኪሞችም ከፍተኛ ምስጋናን አቀርባለሁ »ማለቱን ዘገባው ጨምሮ ገልጿል።

እፀገነት አክሊሉ

Published in መዝናኛ
Tuesday, 06 February 2018 17:22

ከጉባና ሰዳል ጉያ ስር

ከሌሊቱ ሰባት ሰአት ተኩል ሆኗል፡፡በዚህ ውድቅት ሌሊት ተጓዦች አንደኛው ሌላኛውን ከእንቅልፍ እየቀሰቀሱ ናቸው፡፡አንዳንዶቹ ቀልጠፍ ብለው ሲነሱ ሌሎች ግን እንቅልፉ ተጫጭኗቸው ነው መሰል ለመነሳት ጊዜ ወሰደባቸው፡፡
አውቶቡሱ ባምቦ ፓራዳይዝ ሆቴል ፊት ለፊት መብራቱን በረጅሙ አብርቶ ተጓዦችን እየተጠባበቀ ነው፡፡ ተጓዦች ከያደሩበት እስኪሰባሰቡ ድረስ በእድሜ ሸምገል ያሉት የአውቶቡሱ አሽከርካሪ አስፋልት ላይ የአካል እንቅስቃሴ እያደረጉ ናቸው፡፡ አስገረሙን ለአመታት በአሽከርካሪነት ሳይሰሩ እንዳልቀሩ እና ይህም ጠንካራ እንዲሆኑ ሳይረዳቸው እንዳልቀረ እኔና የጉዞ ጓደኞቼ ገመትን ፡፡
ተጓዦቹ አንድ በእንድ ወደ አውቶቡሱ ገቡ፡፡ አሽከርካሪው ሁሉም ተጓዥ መግባቱን አረጋገጡ ፡፡ ልክ ከሌሊቱ ስምንት ሰአት ሲሆን ጉዞ ተጀመረ፡፡ የአሶሳን የሌሊት ቀዝቃዛ አየር ለቀን ጉዟችንን ወደ ምእራብ አቅጣጫ ወደ ሱዳን በሚወሰደው መንገድ አረግን፡፡
እንቅልፉና እና ድካሙ እንደተጫጫነን እየተጓዝን ነው፡፡ድቅድቁ ጨለማ ከአውቶቡሱ ውጪ ስላለው ዙሪያ ገባ ለማየት አላስቻለንም፡፡ብዙ ከተጓዝን በኋላም የአስፓልቱን መንገድ ትተን በስተቀኝ በመታጠፍ ወደ ሰሜን አቅጣጫ የሚወስደውን ጥርጊያ መንገድ ተያያዝነው፡፡ የተውነው መንገድ ወደ ሱዳን የሚወስድ ነው አሉ፡፡
በስተምእራብ ሱዳን፣በሰሜን አማራ ክልልና እንዲሁም በምስራቅ የቢኒሻንጉል ጉሙዟ የዳንጉር ወረዳ ወደሚያዋስኑትና የኢትዮጵያውያን ሁሉ ቀልብ ወደ አረፈበት ጉባ ወረዳ ነው የምንጓዘው፡፡ በዚያ ሌሊት በጎችና ፍየሎች በመንገዱ ዳር ተኝተው ይታያሉ፡፡ በተመለከትነው ነገር በመገረምም በአካባቢው ጅብ ወይም አውሬ የለም እንዴ? ሌባስ እንዴት አይኖርም? ስንል እርስ በርሳችን ተጠያየቅን፡፡
በአካባቢው ከበጎችና ፍየሎች በስተቀር አንድም የቀንድ ከብት አላየንም፡፤በአካባቢው የቆላ ዝንብ በመኖሩ የቀንድ ከብቶች ሊኖሩ እንደማይችሉ ተገነዘብን፡፡ በክልሉ በአብዛኛው እርሻ እየተለመደ የመጣውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው አሉ፡፡እርሻውም የሚከናወነው ፊት በአንካሴና በዶማ አሁን አሁን ደግሞ በጋማ ከብት ነው፡፡
ተጓዦቹ ብዙ በሄዱ ቁጥር ለመድረስ እንደተቃረቡ በመገመት ያንን ታላቅ ስፍራ ለመጎብኘት ጉጉታቸው እንደጨመረ ነው፡፡ ከአራት ሰአት የሌሊት ጉዞ በኋላ ሊነጋጋ ሲል ቦታውን የሚጠቁምና 66 ኪሎሜትር መቅረቱን የሚያሳይ ታፔላ ተመለከትን፡፡ተጓዦች ይህን ሲመለከቱ በቦታው ላይ የደረሱ ያህል የደስታ ስሜት ተነበባቸው፤ ሁሉም በሩቅ ለማየት እንዲያስችላቸው እይታቸውን ወደ ዙሪያ ገባው አደረጉ፡፡
የንጋት ጮራ ፈነጠቀች፡፡ ፀሀይዋ ከአድማሱ ስር ብቅ ስትል እንዴት ታምራለች፡፡ይህን ውብ ትዕይንት ከተጓዦቹ ጋር የነበሩ የፎቶግራፍ ባለሙያዎች በካሜራቸው ለማስቀረት በመኪናው መስኮት በኩል እያነጣጠሩ ናቸው፡፡
አውቶቡሱ በመካከለኛ ፍጥነት እየተጓዘ ነው፡፡ ልክ ከጠዋቱ ሁለት ሰአት ሲሆን ከአዲስ አበባ በአሶሳ 800 ኪሎ ሜትር ርቀት ከሚገኘው ከዚህ ታላቅ ስፍራ ደጃፍ ላይ ደርሰናል፡፡ ከአዲስ አበባ በጎጃም በለስ አርጎ ወደዚህ ታላቅ ስፍራ ለመድረስ ደግሞ 750 ኪሎ ሜትር መጓዝን ይጠይቃል፡፡ ከመጀመሪያው መግቢያ በር ላይ ደረስን፡፡ የጥበቃ ሰራተኞች የይለፍ ወረቀቱን ከተመለከቱ በኋላ እንድንገባ ፈቀዱልን፡፡
በግምት አምስት ኪሎ ሜትር ከተጓዝን በኋላ የኢትዮጵያውያን የማንነት አሻራ ያረፈበትና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰዳልና ጉባ ወረዳ መካከል በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚገኝበትን ስፍራ ከሩቅ ተመለከትን፡፡
ግድቡ ከአካባቢው ግዙፍ ተራራዎች ጋር እየተፎካከረ ነው፡፡145 ሜትር ከፍታ የሚኖረው ይህ ግድብ የሚገነባው በሰዳል እና በጉባ ወረዳዎች መካከል ነው፡፡ የሚኖረው እርዝማኔም 1800 ሜትር ነው፡፡ ከፍታው እየጨመረ በሄደ ቁጥር ስፋቱ የሚቀንስ ሲሆን መጨረሻ ላይ ስምንት ሜትር ስፋት እንደሚኖረውም ነው ከመረጃዎች ለማወቅ የቻልነው፡፡
ከጉብኝታችን በፊት በቅድሚያ ወደ አንድ ትልቅ ካፍቴሪያ አምርተን የቁርስ ግብዣ ተደረገልን፡፡ ቀጥሎም የግድቡ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ቢሮ በመገኘት ግድቡ ስላለበት ደረጃ ገለፃ ተደረገልን፡፡ ገለፃው ግድቡን በአካል ተጠግቶ ለማየት በሁሉም ዘንድ ጉጉት ይበልጥ እንዲያድር አደረገ፡፡
የግድቡ ፕሮጀክት የሚካሄድበት ስፍራ እጅግ ሰፊ እንደመሆኑ የግድቡን የተለያዩ ክፍሎች ለመጎብኘት በእግር ጉዞ የሚሞከር አይደለም፡፡ እኛም በቀረበልን አውቶቡስ በመጓዝ ጉብኝቱን ማድረግ ጀመርን ፡፡ አብዛኛዎቻችን ግድቡ ስለሚገኝበት አካባቢ እና ስለአካባቢው የአየር ሁኔታ መረጃዎችን በማግኘታችን የአካባቢውን ሙቀት ለመቋቋም የሚረዱ ሳሳ ያሉ ልብሶችን ለብሰናል፡፡ እንዲያም ሆኖ ሙቀቱ እጅግ ፈታኝ ነበር፡፡
በመጀመሪያ የግድቡን የግራ ክፍል ጎበኘን፡፡ በርቀት የሚታየውንና ከዚሁ ጋር የሚመሳሰለውን በስተቀኝ በኩል ካለው የግድቡ አካል ጋር የማገናኘት ስራ ብቻ እንደቀረ ተመለከተን፡፡ ከግድቡ በስተግራ አቅጣጫ የሚገኘውን የግድቡን ማስተንፈሻ ጎበኘን፡፡ ይህ ማስተንፈሻ ከግድቡ ዋናዎቹ ማስተንፈሻዎች በተጨማሪ የወንዙ መጠን በጣም ከፍተኛ ሲሆን ለማስተንፈሻነት እንዲያገልግል የተሰራ ነው፡፡
የግድቡን አጠቃላይ ሁኔታ ሲታዘቡ ከነበሩት የስነ ጥበብ ባለሙያዎች የተወሰኑት የመገረም ስሜት ይታይባቸዋል፤ቀሪዎቹ ደግሞ ለማመን ተቸግረዋል፡፡ ስለግድቡ ያላቸው ምስልና አሁን በቦታው መጥተው የተመለከቱት ፍፁም የተለየ ሆኖባቸዋል፡፡ ባለሙያዎቹ የግድቡን አብዛኛውን ክፍል ተዟዙረው ጎበኙ፡፡ ሁሉም ግድቡን በስነ ጥብብ እይታ እንደተመለከቱት እንደሆነ አሰብኩ፡፡
ለዘመናት በራሱ መንገድ ብቻ ሲፈስ የኖረው ታላቁ የአባይ ወንዝ በተዘጋጀለት መንገድ በግድቡ መሃል ለመሃል አቋርጦ እንዲያልፍ ተደርጓል፡፡ ፍሰቱ አሁንም እጅ አልሰጠሁም የሚል ያስመስለዋል፡፡ አባይ ደፍርሶ ይታይል፤ይህም አሁንም ጥቁር አፈር ይዞ እየሄደ መሆኑን ይጠቁማል ፡፡ይህ ሁሉ አፈር ወደ ግብፅ ሲደርስ ግብፃውያንን ምን ያህል ሊመግብ እንደሚችል ገመትኩ ፡፡
ከግድቡ በስተቀኝና በስተግራ በኩል ከኮንክሪት ሙሌቱ ስር ከግድቡ ጫፍ እስከ ጫፍ የሚወስዱ ሁለት በሮች ይታያሉ፡፡ በሮቹ በግድቡ የውስጠኛ ክፍሎች ምናልባት የሚንጠባጠብ ውሃ ካጋጠመ ለመቆጣጠር እንዲያስችል የተገነቡ መሆናቸውን የግድቡ ግንባታ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ አብራሩልን፡፡ ከግድቡ መካከለኛው ክፍል ላይ ቆመናል፡፡ በግራና በቀኝ ያለው ግንባታ የተጠናቀቀ ይመስላል፤ መሃሉን ማገናኘት ይቀራል፡፡
ከሁሉም የግድቡ ክፍሎች የአብዛኛዎቻችንን ትኩረት የሳበው ከግድቡ በስተቀኝ በአስር ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በመገንባት ላይ የሚገኘው ሳድል ዳም የተሰኘው ግድብ ነው፡፡ ይህ ግድብ 5 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ይረዝማል፡፡ ቁመቱም 50 ሜትር ይደርሳል፡፡ ይህን የግድቡን ክፍል ለመገንባት እስከ 130 ሜትር ጥልቀት ድረስ በመውረድ የአለት ምርመራ ተደርጓል ፡፡ የውጪና የሃገር ውስጥ ሰራተኞች ስራውን ለማፋጠን እየተረባረቡ ናቸው፡፡ ግድቡ የሚገነባው ግድቡ የሚይዘው የውሃ መጠን ከሚጠበቀው ከፍታ ሳይደርስ ውሃ በዚህ አቅጣጫ ሾልኮ እንዳይወጣ በሚል ነው፡፡
አብዛኛውን የግድቡን ክፍል ከጎበኘን በኋላ የምሳ ግብዣ ተደረገልን፡፡ ከዚያም ጉብኝቱን አስመልክቶ ጎብኚዎች ለስራ አስኪያጁ ጥያቄዎችን፣ አስተያየቶችን አቀረቡ፤አመሰገኑ፡፡ ስራ አስኪያጁ ለጥያቄዎቹ መልስ ሰጡ፡፡ ለአስተያየቶቹ እና ምስጋናውም አፀፋውን በምስጋና መለሱ፡፡ ጉብኝቱም በዚሁ ተቋጨ፡፡
የአካባቢው ሙቀት እንደ ወላፈን ይጋረፋል፡፡ አውቶቡስ ውስጥ ስንገባ ደግሞ ሙቀቱ ይበልጥ ጨመረ፡፡ ከቀኑ 9 ሰእት ከ 30 ሆኗል፡፡ ይህ ወቅት እና ሰአት በበጋ ወቅት ለአዲስ አበባ እና ለአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል ሞቃት ቢሆንም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሚገነባበት ስፍራ ግን ከዚህ ይለያል፡፡
ሁሉም ይህን ታላቅ ግድብ በስስት እያየ ወደ አውቶቡሱ ገባ፡፡ሁሉም ከጉባና ሰዳል ጉያ ስር ያደረጉት ጉብኝት ያስገኘላቸውን ስንቅ ይዘው ግድቡን ወደ ኋላ በመተው መጓዝ ጀመሩ ፡፡ አውቶቡሳችን የታላቁ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የሚገኝበትን ይህን ታላቅ ስፍራ ወደኋላ ትቶ አዳሩን ግልገል በለስ ለማድረግ በፍጥነት ወደ ሰሜን አቅጣጫ ተፈተለከ፡፡

 አስናቀ ፀጋዬ

Published in መዝናኛ

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2030 በተቀመጡት የዓለም የጤና ግቦችና የሀገራችን የዘርፉ ትራንስፎርሜሽን እቅድ መሰረት የኤች አይ ቪ ና የቲቢ ስርጭትን ለመግታት እንዲሁም ወባን ለማጥፋት እየሰራች መሆኑ ይታወቃል፡፡ የእነዚህን በሽታዎች ስርጭት ለመግታትም ባለፉት አስርት አመታት ሃገሪቱ ከፍተኛ ርብርብ ስታድርግ ቆይታ ውጤቶችንም ማስመዝገብ ችላለች፡፡
እነዚህን የጤና ችግሮች ለመፍታት ሀገሪቱ ከምትመድበው በጀት በተጨማሪ የለጋሾች ድጋፍ ሚና ወሳኝ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ከእነዚህ ለጋሾች መካከልም ግሎባል ፈንድ ይጠቀሳል፡፡ ግሎባል ፈንድ የኤች አይቪ ኤድስና የቲቢን ስርጭት ለመቀነስ እንዲሁም ወባን ለማጥፋት ለሚደረገው ጥረት የገንዝብ ድጋፍ የሚያደርግ ተቀማጭነቱን በሲወዘርላንድ ጄኔቭ ያደረገ ትልቅ አለም አቀፋዊ ተቋም ነው፡፡
ኢትዮጵያም ከግሎባል ፈንድ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ከሚደረግላቸው አገሮች መካከል አንዷ ስትሆን እስካሁን የኤች አይቪንና የቲቢ ስርጭትን ለመከላከል ፣ህሙማንን ለማከምና ለመደግፍ፣ እንዲሁም ወባን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እ.ኤ.አ ከ2002 እስከ 2017 መጨረሻ ድረስ ከ ሁለት ቢለዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ድጋፍ አግኝታለች፡፡
ሃገሪቷ እ.ኤ.አ ከ2015 እስከ 2017 ድረስ ባለው ጊዜ ከግሎባል ፈንድ በአጠቃላይ 474 ሚሊዮን 575 ሺ የአሜሪካ ዶላር ያገኘች መሆኑ ይታወቃል፡፡ይኸው ገንዘብ ለኤች አይቪ እና ቲቢ መከላከልና መቆጣጠር፣ ወባን ለመቆጣጠር እና ለማጥፋት እንዲሁም የጤና ስርዓቱን ለማጠናከር ውሏል፡፡
ባሳለፍናው ሳምንት መጀመሪያ ላይም እ.ኤ.አ ከ2018 እስከ 2021 ሶስቱን በሽታዎች ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም የጤና ስርአቱን ለመደገፍ የሚያግዝ በአጠቃላይ 379 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ በግሎባል ፈንድ ፀድቋል፡፡ ይህ ድጋፍ ቀደም ሲል ከነበረው የገንዘብ ድጋፍ ጋር ሲነፃፀርም በ95 ሚሊዮን 575 ሺ የአሜሪካን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል። ይህም እነዚህን በሽታዎች ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገው የግሎባል ፈንድ ድጋፍ እየቀነሰ መምጣቱን ያመለክታል፡፡
በግሎባል ፈንድ ሶስቱን በሽታዎች ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እንዲቻል የተደረገው የአሁኑ የገንዘብ ድጋፍ ከአለፉት አመታት ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከበደ ወርቁም ይገልጻሉ፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ፤ሃገሪቱ ባለፉት አመታት የጤና ስርአቱን እስከ ታችኛው ማህበረሰብ ድረስ በመውረድ መፈፀም በመቻሏና ውጤቶች በመመዝገባቸው የገንዘብ ድጋፉን አሁንም ማግኝት ተችሏል፡፡ በተለይም የኤች አይ ቪ ስርጭትን በመቆጣጠርና ከኤች አይቪ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን ሞት መቀነስ በመቻሉ የገንዘብ ድጋፉን ማግኘት አስችሏል ፡፡
አሁን ከግሎባል ፈንድ የተገኘው የገንዘብ ድጋፍ በሃገሪቱ የተያዘውን የአምስት አመት የጤና መካከለኛ ዘመን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ማሳካትን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል የተመደበው የገንዘብ መጠን ከሚያስፈልገው የግብአት ፍላጎት አንፃር ሲታይ ዝቅተኛ በመሆኑ እስከ አሁን ስራ ላይ ያልዋለውን ቀሪ ገንዘብ አሁን ከተደረገው ድጋፍ ጋር በማጣጣም መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ከተለያዩ ተራድኦ ድርጅቶች በልገሳ የተገኘውን ገንዘብም በተመሳሳይ ስራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል፡፡ ይህን ውስን የገንዘብ ድጋፍ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ ባለሙያዎች ውጤታማ አጠቃቀምን ተግባራዊ በማድረግና በመዘርጋት በፕሮግራሙ መሰረት የተቀመጡ የጤና ግቦችን ለማሳካት እንዲቻል ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል፡፡
የአለም አቀፉ ማህበረሰብ የተራድኦ ድርጅቶችና የለጋሽ ሃገራት መሰላቸት ለድጋፉ ማነስ ምክንያት መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰው፣ትልቁ ሃብት ጠንካራ የጤና ስርአት መገንባት መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ውጤታማ የገንዘብና የቴክኒክ አጠቃቀምን ማሻሻል እንደሚያስፈልግም ያስገነዝባሉ፡፡
በጤና ጥበቃ ሚኒሰቴር ሀገር አቀፍ የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ ወይዘሮ ህይወት ሰለሞን እንደሚገልፁት፤ የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከግሎባል ፈንድ 112 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ ተገኝቷል፡፡በዚህ ገንዘብም በዋናነት ህብረተሰቡን ያሳተፉ ወባን የመከላከል ስራዎች ይሰራሉ፡፡ ከእነዚህ ስራዎች ውስጥም ህብረተሰቡ ራሱን ከወባ በሽታ እንዲከላከል የአጎበር ስርጭት ይካሄዳል፡፡ ህብረተሰቡ አጎበሮችን በአግባቡ እንዲጠቀም የማስተማር ስራዎችም ይሰራሉ፡፡ ለርጭት በተመረጡ ቦታዎች ላይ የቤት ለቤት የፀረ ወባ ርጭት ይካሄዳል፡፡ ተከታታይነት ያላቸው የወባ ፕሮግራም ስልጣናዎችም ለጤና ባለሙያዎች ይሰጣሉ፡፡
ከወባ በሽታ ጋር በተገናኘ የሚሰሩ ስራዎችን ለማስፈፀም ከግሎባል ፈንድ የተገኘው ገንዘብ በቂ ያለመሆኑን የሚጠቅሱት ወይዘሮ ህይወት፤ በተለይ ወባን መከላከልና ማጥፋት የአንድ ዘርፍ ስራ ብቻ አለመሆኑን ይጠቅሳሉ፡፤ ስራው በቅንጅትና ሁሉንም ዘርፎች ባሳተፈ መልኩ የሚሰራ ስራ መሆኑን ጠቅሰው፣ለዚህም ብዙ ገንዘብና ሃብት ይጠይቃል ይላሉ፡፡ ይህ በመሆኑም ከአጋር ድርጅቶችና ከሃገር ውስጥ የሃብት ምንጮች የተገኘውን ገንዘብ በማቀናጀት ስራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግ ያመለ ክታሉ፡፡
እንደ ወይዘሮ ህይወት ገለፃ፤ ለወባ መከላከል ስራ እኤአ ከ2017 እስከ 2020 የሚያሰራ ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጅቷል፡፡ በእቅዱ መሰረት ወባን ለመቆጣጠርና ለማጥፋት 500 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም በተለያየ ምክንያቶች ለጋሾች የሚሰጡት ገንዘብ በመቀነሳቸው በአሁኑ ወቅት የተገኘው የገንዘብ ድጋፍ 112 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡
ወይዘሮ ህይወት ይህን ያህል የገንዘብ ድጋፍ መገኘቱንም በአድናቆት ነው የተመለከቱት፡፡ ሃገሪቷ የወባ በሽታን ስርጭት ከ50 በመቶ በላይ እንዲሁም በወባ በሽታ የሚከሰት የሞት መጠንን ድግሞ ከ60 በመቶ በላይ መቀነስ መቻሏን በመጥቀስም፣ ወባን ለማጥፋት ያደረገችው ጥረት ለድጋፉ አስተዋፅኦ አደርጓል ይላሉ፡፡ድጋፉ በቂ አለመሆኑንም በመግለጽ ሌሎች አጋር ድርጅቶችንና ከፌዴራል መንግስትና ከክልል አስተዳደሮች የሚመደብ በጀትን በማጣመር ስራ ላይ ማዋል ይጠይቃል ይላሉ፡፡
ከወባ ጋር በተያያዘ የሚከናወን ተግባር በፋይናንስ ካልተደገፉ ውጤት እንደማይመጣ የሚጠቅሱት ወይዘሮ ህይወት፣ ገንዘቡን በበጀት ይዞ የተፈለገውን ስራ በወቅቱ ለማካሄድ ገንዘቡን በአግባቡ ስራ ላይ ማዋል እንደሚገባም ያመለክታለ፡፡ ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን በሽታውን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንፃር የተገኙ ስኬቶችን ማስቀጠል እንደማይቻል ያስገነዝባሉ፤በወባ በሽታ የሚደርሰው ህመምና ሞት ሊጨምር እንደ ሚችልም ያሳስባሉ፡፡
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት የቲቢና ስጋ ደዌ ኬዝ ቲም አስተባባሪ ዶክተር ብሌን አየለ እንደሚሉት፤ ለቲቢ በሽታ መከላከል ስራ የሚሆንና ለሶስት ዓመት የሚያገለግል የ46 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ከግሎባል ፈንድ ተገኝቷል፡፡ ይህም ገንዘብ በዋናነት በቲቢ በሽታ የሚጠቁ ሰዎችን ቁጥር አሁን /እ.አ.አ በ2018/ ካለበት 192 በመቶ ሺህ ህዝብ እ.ኤ.አ በ2021 161 ለማድረስ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ስራ ላይ ይላል፡፡
እንደ ወይዘሮ ብሌን ገለፃ ፤በአሁኑ ወቅት ለቲቢ በሽታ መከላከል ስራ የተደረገው የገንዘብ ድጋፍ በቂ የሚባል ባለመሆኑ የተለያዩ አጋር ድርጅቶች የሚያደርጉትን ድጋፍና ከመንግስት የሚገኘውን በጀት በማጣመር መስራት ያስፈልጋል፡፡
በግሎባል ፈንድ ብቻ ከ2015 እስከ 2017 እ.ኤ.አ ለቲቢ በሽታ መከላከል ስራ የተመደበው ገንዘብ ወደ 58 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚጠጋ እንደነበርም አስተባባሪዋ አስታውሰው፣ ከ2018 እስከ 2021 እ.ኤ.አ የተደረገው የገንዘብ ድጋፍ ቀንሶ ወደ 46 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወርዷል፡፡
በተለያዩ መንገዶች የሚገኙ ድጋፎችን በማስተባበር ከባለፈው ዓመት ወደ ዘንድሮው በጀት አመት የተዘዋወረውን ገንዘብ አሁን በተደረገው ድጋፍ ላይ በመጨመር መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ለቲቢ በሽታ መከላከል የሚረዱ መሳሪያዎችን ግዢዎችን ለማጣጣምና ያለውን ክፍተት ለመድፈንም ገንዘቡን በአግባቡ መጠቀም ይገባል፡፡ ይህም ሙሉ በሙሉ በቂ ባለመሆኑ ከመንግስት የሚደረገውም ድጋፍ በተቻለ መጠን አካቶ መስራትን ይጠይቃል፡፡
የስራ ሃላፊዎቹ እንዳሉት ከግሎባል ፈንድ የተገኘው የገንዘብ ድጋፍ ባለፉት አመታት ከተደረገው ጋር ሲናጻጸር ቀንሷል፡፡ይህም በሽታዎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም ባለፉት አመታት በተከናወኑ ተግባሮች በበሽታዎቹ ላይ የተመዘገበውን ስኬት ለመጠበቅ ውጤታማ የገንዘብ አጠቃቀምን ተግባራዊ ማድረግ እና ሌሎች ድጋፎችን ማፈላለግን ይጠይቃል፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

 

Published in ማህበራዊ

በአገሪቱ የፍትህ ስርዓት ላይ ፖሊስ ፣ አቃቤ ህግ እንዲሁም በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች የየራሳቸው ሚና አላቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት በቅንጅትም ይሁን በተናጥል የሚያከናውኗቸው ተግባራት የአገሪቱን የፍትህ ስርዓት ይገልጻሉ፡፡ የአንደኛው ተቋም መድከም አልያም መጠንከር በሌላኛው ላይ አሉታዊ እንዲሁም አዎንታዊ ተጽእኖ ያሳርፋል።
በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከሚከታተላቸው 14 ተቋማት መካከል የዴሞክራሲ ተቋማት በሆኑት በፍትህ ተቋማት ላይ ያደረገውን የመስክ ምልከታ አስመልክቶ ሰሞኑን ከተቋማቱ ጋር ተወያይቷል፡፡
በፍትህ ተቋማት የቅንጅታዊ አሰራር ክፍተት ምክንያት ሃሰተኛ ማስረጃዎችና ሰነዶች፣ ደረቅ ቼክ፣ ታክስ ማጭበርበር፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር እንዲሁም ኮንትሮባንድ የፍትህ ሥርዓቱን በማዛባት በግለሰቦችና በመንግሥት ሃብት ላይ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚባክንበትን ሁኔታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር አለመቻሉን ቋሚ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡
በሀይል ድርጊት ወይንም በማስገደድ መረጃን ለማግኘት ጥረት እንደሚደረግ፣ በተጠርጣሪዎች ላይ ማስረጃ በሚታጣበት ወቅት ወደ ፍርድ ቤት ሳያቀርቡ ለረጅም ዓመታት ታስረው እንዲቆዩ እስከ ማድረግ የሚደርሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲሁም በአፋጣኝ ፍትህን ያለማግኘት ችግሮች እየተስተዋሉ መሆናቸውንም በመስክ ምልክታው ማረጋገጡን ቋሚ ኮሚቴ አመልክቷል፡፡
ወይዘሮ ጥሩዬ ጤናው እንደተናገሩት፤ የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ለ1 ሺ 900 የቀጠሮ ታራሚዎች ማቆያነት የተገነባ ቢሆንም አገልግሎት እየሰጠ ያለው ከ 3 ሺ ለሚበልጡ ሰዎች ነው ።በዚህ የተነሳም ታራሚዎች አንድ ባለ 90 ሳንቲ ሜትር ፍራሽ ለሁለት ለመጋራት ተገደው የነበረ ሲሆን፣ በእዚህ ዓመት ችግሩ ገዝፎ ሁለት ተመሳሳይ ስፋት ያላቸውን ፍራሾች በማገጣጠም 5 ሰዎች እንዲተኙ እየተደረገ ነው ፤ሌሎች ደግሞ አንዱ በአንዱ ላይ ተነባብሮ መሬት ላይ ለመተኛት ተገደዋል።
በአንድ ክፍል ውስጥ ከ200 በላይ ታራሚዎች ታምቀው እንደሚገኙ ወይዘሮ ጥሩዬ ጠቁመው፣ በዚሁ ክፍል ውስጥ ሶስት መቀመጫ ብቻ ያለው መጸዳጃ ቤት መዘጋጀቱን በዓይናቸው ተመልክተው ማረጋገ ጣቸውን ለቋሚ ኮሚቴው አብራርተዋል።ይህን ሁኔታ ያባባሰው ፍትህ በፍጥነት ያለማግኘት ችግር መሆኑንም ይጠቁማሉ።
ወይዘሮ ጥሩዬ የፍትህ ስርዓቱ ፈጣን ያለመሆኑን በማሳያ ሲያቀርቡም በቀጠሮ ማረፊያ ቤት ውስጥ ያለፍርድ ታስረው የሚገኙ ሰዎች ከ4 ዓመት በላይ 17 ፣ ከ 3 ዓመት በላይ 159፣ ከ2 ዓመት በላይ 643 እንዲሁም ከ 1 ዓመት በላይ 230 መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡
« ችግሩን መፍታት ለምን አልተቻለም » የሚለው ሊያሳስብ ይገባል ያሉት ወይዘሮ ጥሩዬ ከእናንተ እየተሰጠ ያለው መልስ መረጃና ማስረጃ ላይ እየተመሰረትን ነው ወደ ክስ የምንገባው የሚለው ሊሆን ይችላል ሲሉ ከፍትህ አካላቱ ሊሰጥ ይችላል ያሉትን አስተያየት ተናግ ረዋል፡፡መረጃውም ማስረጃውም እያለና ወደ ክስ ተገብቶም ውሳኔ ለመስጠት የማይቻልበት ሁኔታ ግን አሁንም መፍትሄ እንደሚፈልግ ይናገራሉ።
በሌላ በኩልም ጠቅላይ አቃቤ ህግ ከተሰጡት ሀላፊነቶች መካከል ታራሚዎች ድረስ በመው ረድና ችግሮቻቸውን በመቀበል መፍትሔ መስጠት ነው፤ ነገር ግን ተቋሙ ሀላፊነቱን እየተወጣ ስላለመሆኑ እኛም ታዝበናል፤ ተጠርጣሪ እስረኞችም አረጋግጠውልናል፤ተቋሙ ሀላፊነቱን ላለመወጣቱ ምክንያቱ ምንድንነው የሚለውም መፍትሄ ሊቀመጥለት ይገባል ይላሉ።
«ፖሊስ ምርመራ በሚያደርግበት ወቅት የዜጎች ሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ የሚታዩ ጥቃቅን ነገሮችን መነሻ በማድረግ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ሊያራምዱ የሚፈልጉ አካላት እንዳሉ እኛም እንጋራለን›› ያሉት ወይዘሮ ጥሩዩ፤ ችግሮቹን በልኩና በሚዛኑ ማየት እንደሚገባምይገልጻሉ።
ከታራሚዎች አልፎ ህዝቡ በሙሉ እየተናገረ ያለውን ሀቅ በጥቃቅን መፈረጁ በአንድና በሁለት ሰዎች መገደቡ እንደማይ ጠቅም አስታውቀው፣ ጉዳዩ አሳሳቢ ለስርዓቱም አደጋ እየሆነ መምጣቱን በአግባቡ መመልከትና ውስጥን መፈተሹ ጥሩ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ችግሩ ጭራሽ የሌለ ማድረጉ አይጠቅምም ሲሉም ያስገነዝባሉ።
ወይዘሮ ጥሩዬ የሴቶችና ወንዶች ማረሚያ ቤቶች መቀራረብ ከዚህም አልፎ በስልጠና ላይ አብረው እንዲውሉ መደረጉ ስነ ልቦናዊ ጫናው ከግምት የገባ አይመስልም ይላሉ፡፡በተለይም በቀላሉ የሚፈቱ ችግሮችን አመራሩ በአብይ ኮሚቴውም ይሁን በቅንጅት ኮሚቴው ማየት ለምን አልቻለም? ወይንስ ችግሩ የማረሚያ ቤቱ ብቻ ነው ብለን ትተነው ነው? ሲሉም ጠይቀዋል። ችግርን የጋራ አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይም ሊታሰብበት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።
ለታራሚዎች ይቅርታ የማድረግ ሀላፊነት የተሰጠው አቃቤ ህግም ሚናውን በሚገባ እየተወጣ አይመስልም ሲሉም ወይዘሮ ጥሩዬ ተናግረዋል፡፡ ለዚህ አባባላቸው መነሻ የሆኗቸውም በማረሚያ ቤት ውስጥ የ96 ዓመት አዛውንት በሰው እርዳታ ስር ሆነው መገኘታቸው እንዲሁም ለጥበቃም ለቁጥጥርም የሚያስቸግሩ የአእምሮ ህሙማን መኖራቸው ነው፡፡ ቋሚ ኮሚቴው ይህንንም ባደረገው ኢ-መደበኛ ምልከታ ወቅት መታዘቡን ተናግረዋል፡፡
የአሰራር ስርዓቱ እነዚህን ሰዎች ለመልቀቅ የማይፈቅድ ቢሆን እንኳ በተጨባጭ በአይናችን የምናየው የጎላ ችግር በመሆኑ ብቻ ህጉን አሻሽሎም ይሁን ሌሎች መፍትሔዎች ተፈልገው እነዚህን ሰዎች በይቅርታ ወደሚፈለገው ቦታ ማዘዋወሩ ለምን ትኩረት ተሰጥቶ አይሰራም ይላሉ።
እንደ ወይዘሮ ጥሩዬ ማብራሪያ ፤ከውጭ ዜጋ ታራሚዎች ጋር በተያያዘ ባነሱት ሀሳብም በተለይም ታራሚዎቹ ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ዘመዶቻቸውን የሚገናኙበት የስልክ አገልግሎት ከማመቻቸት አንዳንዶቹ ቅያሪ ልብስ ከመፈለግ ሌሎቹ ደግሞ ከምግብ ጋር የሚያነሷቸው የተለያዩ ጥያቄዎች አሉና እነዚህንም በመመለሱ በኩል ከፍተኛ የሆነ እጥረት ይታያል፤ ይህ ደግሞ የአገርንም ገጽታ የሚጎዳ በመሆኑ በከፍተኛ ትኩረት ሊሰራበት ይገባል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ነጋ አደሬ በፖሊስ ተቋማት አካባቢ ስላለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ለቋሚ ኮሚቴው በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፤ በመጀመሪያ ሊታይ የሚገባው ተጠርጣሪ እንዴት ይያዛል የሚለው ነው፤ አንድን ተጠርጣሪ ለመያዝ የተቀመጠ መመሪያ (ማንዋል) አለ፤ በመመሪያው መሰረትም ጥቆማ በተደረገበት ሰው ላይ የተለያየ ዓይነት ክትትል ይደረጋል፡፡ ሰውየው እውነት ችግሩን አድርሷል ወይ? የሚለው መረጃም እስከሚገኝ ድረስ ክትትሉ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል፡፡ ቅድመ ሁኔታዎቹ በሚገባ ከተጠናቀቁ በኋላ ጥፋተኛ የሚያደረገው መረጃ ከተገኘ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማውጣት ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ ይሰራል ።
ቀጣዩ ስራ የሚሆነው በቁጥጥር ስር በዋለው ተጠርጣሪ ላይ ተጨማሪ መረጃዎችን የማስፋት ስራ ሲሆን፣ በሚገባና በዝርዝር ከታየ በኋላም ምናልባት ወደ ሌሎች የሚሰፋ ከሆነም እየሰፋና የጊዜ ቀጠሮ በህጉ መሰረት እየተጠየቀ የወንጀሉን ስር ለማግኘት በርካታ ተግባራት ይከናወናሉ፡፡ ከዚያም ወደ አቃቤ ህግ ተልኮ ክስ ይመሰረታል፡፡
‹‹በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ የሰብዓዊ መብት ይረገጣል፣ ተጠርጣሪን አስገድዶ ቃል መቀበል ይፈጸማል ፤ የሚባሉ ነገሮች ይሰማሉ፡፡እነዚህ አስተያየቶች በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይም ሲወጡ ይታያል፡፡›› ሲሉ አቶ ነጋ ይገልጻሉ፡፡
መመሪያው (ማንዋሉ) በግልጽ የሚያስቀምጠውና ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ የተጠርጣሪን ሰብዓዊ መብት መጠበቅ ላይ ነው። እያንዳንዱ መርማሪም መመሪያው በእጁ ያለ በመሆኑ ምን መስራት እንዳለበትና እንደሌለበት የትኛው ተግባሩ ተቀባይነት ያለውና የሌለው መሆኑን እንዲሁም ችግር ፈጥሮ ሲገኝም እንደሚያስጠይቀው ጠንቅቆ ያውቃል ይላሉ።
‹‹ፖሊስ ሲባል አዲስ አበባ ላይ ብቻ ያለ አይደለም በመላው አገሪቱ በተለያዩ ክልሎችም ፖሊስ አለ ›› ያሉት አቶ ነጋ፤ እንደ የግለሰቡ ስነምግባርና ሁኔታ የሚፈጠሩ ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉም ይገልጻሉ፡፡ይህም ቢሆን ይቅር የሚባል ተግባር እንዳልሆነም ያብራራሉ።
‹‹የምርመራ ስራ ከተጠርጣሪው በልጦ መገኘት እንደመሆኑ ለመርማሪዎች የተለያዩ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች በየጊዜው ይሰጣል። ሆኖም እየተነሱ ያሉ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች ግን ፍጹም እንዳይነሱ ማድረግ አልተቻለም፤ በተቻለ መጠን ግን ችግሮችን ለመቀነስ ስራዎች ይሰራሉ ሲሉ ይገልጻሉ።
በዚህ ደረጃ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ለአብነት ያህልም የምርመራ ስራው በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን የማድረግ ጅምር መኖሩን ጠቅሰው የምርመራ ሂደቱ በአጠቃላይ በቪዲዮ እንዲቀረጽ እየተደረገ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
አቶ ነጋ እንዳብራሩት፤በቋሚነት በየሳምንቱ ሰኞ የሚመለከታቸው ዳይሬክቶሬቶች ሙሉ ጊዜያቸውን ታራሚዎችን በማነጋገር እንዲያሳልፉ ይደረጋል፤ተጠርጣሪ እስረኞችም ሊስተካከሉ የሚገባቸው ጉዳዮች ፣ የሚፈልጉትን ነገር ፣ በደሎች ደርሰው ከሆነም እንዲናገሩ እድል ይሰጣል፡፡ በዚህም ችግሮቹን ተቀምጦ በመገምገም ባለቤት የመስጠት በቀጣዩ ሰኞ ችግሮቹ ሙሉ በሙሉ የሚፈቱበትን ሁኔታም የማመቻቸት ተግባር እየተከናወነ ይገኛል፤በዚህም ውጤት እየታየ ነው።
በአብዛኛው በእስረኞች የሚነሳው ጥያቄ ቤተሰቤን በስልክ ልገናኝ የሚል ነው የሚሉት አቶ ነጋ፣ ይህም እንዲፈጸም መጥተው ማየት የሚችሉ ቤተሰቦችም የጉብኝት ፕሮግራም እንደሚመቻችላቸው ተደርጓል ይላሉ፡፤የጊዜ ቀጠሮ ረዝሞብናል የሚል ጥያቄን ለሚያነሱ ተጠርጣሪዎችም የምርመራ ሂደቱ የት እንደ ደረሰ የማስረዳት አካሄድ እንዳለም ያመለክታሉ።
እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ፤ የተጠር ጣሪዎችን ሁኔታ ለመመልከት ለሚመጣ ማንኛውም አካል በሩ ክፍት ነው፡፡በተያዘው ዓመት ብቻም አምስት ጊዜ የሱፐርቪዥን ተግባር ተከናውኗል። በእኒዚህ ሱፐርቪዥኖችም እስከ ውስጥ ድረስ ገብቶ የመጎብኘትና የማነጋገር መብት ተሰጥቷል፡፡ አንዳንድ ጎብኚዎችም የሰጧቸው አስተያየቶች ጥሩ ሆነው ተገኝተዋል።
ይህም ሆኖ ችግሮች መኖራቸው እንደ ማይቀርም አቶ ነጋ ይጠቁማሉ፡፡ በተለይም ከሰብዓዊ መብት አያያዝ ጋር ተገናኝቶ በምርመራ ስራዎች ላይ ለሚፈጠሩ ነገሮች ዋስትና መስጠት አይቻልም ይላሉ።
‹‹ችግሮች ተፈጠሩ በሚል ዝም ብሎ ማውራት ሳይሆን የት ተፈጠረ? በማን ተፈጠረ?›› የሚለውን አጣርቶ ተጠያቂ መሆን ያለበትን ማስጠየቅ እንጂ በተለይም በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ ስም እየተጠቀሱ የሚናፈሱ ወሬዎች በጣም ሞራል የሚነኩና ሊታዩ የሚገባቸው መሆናቸውን ነው ያስታወቁት።
‹‹በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ እየተነሱ ያሉ ነገሮች ፖሊስን የሚገልጹ አይደሉም፤ በግለሰብ የሚደረጉ ተግባራት ሊኖሩ ይችላሉ፤ ይህ የአስተሳሰብ ችግር ነው ›› ሲሉ ያመለክታሉ።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ በላቸው አንሻሶ በሰጡት ምላሽ ረጅም ዓመታት ያለምንም ፍርድ በማረሚያ ቤት የቆዩ ታራሚዎችን ቁጥር ለመቀነስ ከማረሚያ ቤት አስተዳደር ጋር በመነጋገር ከ221 በላይ የሆኑ ከሁለት ዓመት በላይ የታሰሩ ሰዎችን ጉዳዮች በመለየትና ክረምቱን በሙሉ ማስረጃ በመስማት ለ113ቱ ውሳኔ መስጠት ተችሏል። በተያዘው ዓመትም ረጅም እድሜን ያስቆጠሩና ለአገራዊ ገጽታ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸውን ጉዳዮች በመለየት እልባት እንዲያገኙ የማድረጉ ስራ ይቀጥላል።
የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ዋና ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ ረጋሳ የቋሚ ኮሚቴው አባል ወይዘሮ ጥሩዬ ባነሷቸው ሀሳቦች እንደሚስማሙ ይገልጻሉ፡፡ ችግሩም እንደሚስተዋል ተናግረው፣ የታራሚዎች መጨናነቅንም ለመፍታት የተለያዩ ተጨማሪ ግንባታዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ያመለክታሉ፡፡ ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታ ደረጃውን የጠበቀ ማረሚያ ቤት እየተገነባ መሆኑንም ተናግረዋል።
አቶ ደሳለኝ እንዳሉት፤ በዳኞች ውሳኔ አሰጣጥም ሆነ በአቃቤ ህግ በኩል የተነሱ ችግሮች እንደተጠበቁ ሆነው ማረሚያ ቤቱን ለታራሚዎች ምቹ ለማድረግ ምንም ዓይነት የተለየ በጀት ሳይመደብ አንዳንድ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡የሴትና የወንድ ታራሚዎችን ችግር ለመፍታትም የሴቶች ማደሪያ ክፍል በአዲስ መልክ ተሰርቶ በአሁኑ ወቅትም አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
የማሰልጠኛ ተቋምን መለየት እንደማ ይቻል፣ ይደረግ ቢባል እንኳን ለአስርና ከዚያ ለማይበልጡ ሴቶች አንድ የትምህርት ተቋም መክፈት እንደማይቻል አስታውቀዋል፡፡ ወደፊት በሚሰራው አዲስ ህንጻም ችግሩ እንደሚፈታም ይጠቁማሉ።
የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬ በቀረበው የመስክ ምልከታ ላይ በሰጡት ምላሽ እንዳሉት፤ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ጋር ተያይዞ የተነሳውን ችግር ለማረም በአሁኑ ወቅት የማረፊያ ቤቶች ግንባታ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ግንባታው ሲጠናቀቅ ጥያቄው ይመለሳል፤
‹‹ ጥፋተኛን ሰው ገና ለገና መጨናነቅ አለ ብሎ መልቀቅ የማይታሰብ ነው›› ሲሉ አቶ ጌታቸው ያስገነዝባሉ፡፣ አቃቤ ህጉ እንዳሉት፤የቀጠሮ ታራሚዎች ወይም ተጠርጣሪዎች ቁጥርን የመቀነስ ጉዳይ ከሶስት ነገሮች ይመነጫል፡፡ እነዚህም አቃቤ ህግ ተገቢ ምስክሮችን አቅርቦ በማሰማት ሂደት ላይ የሚፈጠር መጓተት፣ ፍርድ ቤቶች ባሏቸው ችሎቶች አጫጭር ቀጠሮ እየሰጡ ፈጣን እልባት አለመስጠታቸው፣ በተጠርጣ ሪዎች የሚቀርቡ የምስክሮች ብዛት ናቸው ። እነዚህ ችግሮች ታይተው እንዴት እልባት ያግኙ የሚለው በቀጣይ ሊታሰብበትና ስርዓት ሊበጅለት የሚገባ ነው።
አቃቤ ህግ ታራሚዎችንም ሆኑ የፖሊስ ጣቢያዎችን እንደሚጎበኝ ጠቅሰው፣ በሚፈለ ገውና በተሟላ መልኩ ሁሉም ማረሚያ ቤቶችና ፖሊስ ጣቢያዎች ተጎብኝተዋል ማለት እንደማይቻልም ተናግረዋል፡፡በተጎበኙት ላይ የታዩ ችግሮችን በመለየት የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ የሚደረግ መሆኑን፣ በ6 ወር ውስጥም ከ 6ሺ በላይ ጉብኝቶች ለማድረግ መቻሉን አቶ ጌታቸው አስታውቀዋል ።
የሴቶች ማረሚያ ክፍሎች ከወንዶች ጋር መገናኘቱ የህንጻው ግንባታ ሲያልቅ እንደሚፈታ በመግለጽ የአቶ ደሳለኝን ሀሳብ ያጠናክራሉ፡፡ ‹‹የ94 ዓመት አዛውንት ታራሚ ቢኖሩም ይቅርታ አሰጣጡ የእድሜ ወሰን አላስቀመጠም›› ያሉት አቶ ጌታቸው፤ ታራሚውን ለማረም አስቸጋሪ የሆነ በጥበቃ ስራውም ላይ ችግር የፈጠረና በሌላው ታራሚ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ካለ እንዲለዩ በማድረግ የሚለቀቁ እንዳሉም ያብራራሉ። ግለሰቡ አዛውንት ስለሆኑ፣ የአእምሮ በሽተኛ ተብሎ በዘፈቀደ የሚለቀቅ ታራሚ እንደማይኖርም ያመለክታሉ፡፡
የህግ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተሾመ እሸቱ በማረሚያ ቤቶች አካባቢ ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ በዓይናችን ያየነውን ሀቅ ነው ይላሉ፡፡ በደረሰባቸው ድብደባ በህክምና እስከ ሶስት ወር ድረስ ሲረዱ ቆይተው ቁስላቸው ሲድን ወደ ቂሊንጦ የሄዱ ሰዎችን ማግኘታቸውንም ይገልጻሉ።
ምናልባት ይህን የሚያደርገው አንድ ሁለት አልያም ሶስት ፖሊስ ሊሆን ይችላል፤ ያሉት ምክትል ሰብሳቢው፣ ምክትል ኮሚሽነሩ ያሉትን እንደማይቀበሉት ተናግረዋል፡፡ የሰብዓዊ መብት እጅግ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑንም በመጥቀስ፣ በዘፈቀደ መታለፍ እንደሌለበት ያመለክ ታሉ፡፡ጉዳዩ ሀቅ መሆኑንም ጠቅሰው፣በዚህ ላይ ሁሉም በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በምክር ቤቱ ጉዳዩ መነሳቱ ካለፉት ስህተቶች ትምህርት መውሰድ እንዲቻል ነው እንጂ እስከ አሁን የተደረገውን ለመቁጠር አይደለም ያሉት ምክትል ሰብሳቢው፣ ዋናው ቁጥሩ ሳይሆን ችግሩ መኖሩን ተማምኖ ለመፍትሔው መረባረብ መቻል መሆኑንም አስታውቀዋል።

 

እፀገነት አክሊሉ

Published in ፖለቲካ

እ.ኤ.አ. በ2014 የተደረገ የኢትዮጵያ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ ጥናት እንደሚያመለክተው፤ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በመሀል ተዘንግተዋል፡፡የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ከአነስተኛ ገንዘብ አቅራቢ ድርጅቶች የፋይናንስ አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ ትላልቅ ኢንተርፕራይዞችም ባንኮች ያግዟቸዋል፡፡ በመካከል የሚገኙት እነዚህ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ግን የብድር አገልግሎት የሚሰጣቸው ተቋም ባለመኖሩ ተዘንግተው ቆይተዋል።
ይህ ችግር በተለይ ከ2007 ዓ.ም. ወዲህ ጎልቶ መጥቷል፡፡ በመሆኑም ከሁለት ዓመት በፊት በተደረገው የብድር ስምምነት መሠረት የ276 ሚሊዮን ዶላር (በወቅቱ ምንዛሪ ዋጋ የ7ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር) በጀት የተያዘለት ማሽነሪ ኪራይ ፕሮጀክት ተነድፎ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት በየክልሉ በተቋቋሙ አክሲዮን ማህበራትና በልማት ባንክ በኩል ከፍተኛ በጀት ተመድቦ የማሽን ሊዝ ፋይናንስ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ፡፡ከዚህ ጋር ተያይዞም በካፒታል ዕቃ ሊዝ ፋይናንስ አፈጻጸም ላይ የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ ከክልሎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ሰሞኑን ግምገማ አካሂዷል።
ከተሳታፊዎቹ መካከልም የአዲስ የካፒታል እቃ ፋይናንስ ንግድ ሥራ አክሲዮን ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ መሳይ ኢንሴኔ፣የሊዝ ፋይናንስ አገልግሎቱ አዲስ መሆኑን በመጥቀስ፣ በአሁኑ ወቅት በተሻለ ሁኔታ እየሄደና የኢንተርፕራይዞችም አብሮ የመስራት ፍላጎት እየጨመረ መሆኑን ይናገራሉ።
እንደ አዲስ ካፒታል፤ በአሁኑ ወቅት ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ማሽኖችን ለኢንተርፕራይዞች ያስተላለፈበት ሁኔታ እንዳለና በቀጣይም ከ76 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ማሽኖች በግዢ ላይ መሆኑን በመግለጽ ኢንተርፕራይዞቹም አገልግሎቱን በበቂ ሁኔታ ለማግኘት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ያስረዳሉ።
እስከ አሁን ባለው ሥራም ጥሩ ውጤት እያሳየ ለመሆኑ ማሳያው በአልባሳት፣ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ላይ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ከቀድሞው አሰራር በተለይም በቴክኖሎጂ ሽግግር በኩል አንድ እርምጃ ወደፊት እንዲራመዱ ያደረገበት ሁኔታ ያለ ሲሆን፣ የተሻለ ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ማምረታቸውም በገበያው ላይ ተመራጭ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።
በብድር አመላለስ በኩልም ከፍተኛ ውጤታማነት እንደሚታይ ተናግረው፤ ብድራቸውን መመለስ ያልቻሉትም ቢሆኑ በሥራ ላይ የጥሬ እቃ አቅርቦት በአገር ውስጥም በውጭም ስላጋጠማቸው በጊዜው መሸፈን ሳይችሉ መቅረታቸውን ይገልጻሉ ። ‹‹ከ 98 በመቶ በላይ ያለው የብድር አመላለስ ጤናማ ነው ማለት ይቻላል›› ሲሉ ጠቅሰዋል።
አቅራቢው፣ ተጠቃሚውና ፋይናንስ አድራጊው ተቋማት አገልግሎቱን የሚያሳልጡ ናቸው። በአሁኑ ወቅት አክሲዮን ማህበሩ ሥራውን በአግባቡ እንዳይሰራ በተለይ በአቅራቢዎች በኩል አስቸጋሪ ሁኔታ ማጋጠሙን ሥራ አስኪያጁ ይናገራሉ፡፡ ይህ ችግር ኢንተርፕራይዞች ማሽነሪ በሚፈልጉበት ወቅት እንዳይቀርብላቸው እያደረገ ነው ይላሉ፡፡ በመንግሥት ተጠንቶ የተያዘው ለአንድ ኢንተርፕራይዝ የማሽን መግዢያ የተያዘው አንድ ሚሊዮን ብር አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ይህም በሥራው ላይ ተግዳሮት መፍጠሩን ይጠቅሳሉ።
አገልግሎቱ በስፋት ያለመተዋወቁም ሥራው ከዚህ በላይ እንዳያድግና እንዳይሰፋ እንቅፋት መሆኑን ገልጸው፤ ከፍተኛ የማስተዋወቅና ኢንተርፕራይዙም በፍላጎት ወደ ሥራው እንዲመጣ የማድረግ ሥራም ገና የሚቀረው እንደሆነ ያብራራሉ።
«አደጉ የምንላቸው አገሮች ለማደጋቸው ዋናው ምክንያት ይህን መሰሉን አካሄድ በመከተላቸው ነው፤ እንደ እኛ አገር ጅምር ሥራም ውጤታማነቱ የምንፈልገውን የኢንዱስትሪ ሽግግር በማምጣቱ በኩልም ምንም ጥርጥር የሌለው ነው፤ ይህም ብቻ ሳይሆን ቁጠባን በማበረታታት በኩልም የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም» ይላሉ።
የአማራ ክልሉ ዋልያ የካፒታል እቃ ፋይናንስ ንግድ ሥራ አክሲዮን ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንዳለ ጌታሁን በበኩላቸው እንደሚሉት፤ አክሲዮን ማህበሩ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የማምረቻ መሳሪያዎችን በመግዛት በኪራይ እየሰጠ ይገኛል። ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ባከናወነው ተግባሩም አፈጻጸሙ ከ747 በላይ ኢንተርፕራይዞችን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል፡፡
በዚህ ሥራ ደግሞ ኢንተርፕራይዞቹን ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር እያንዳንዳቸው ቢያንስ ለአራት ሰው የሥራ ዕድልን በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። በሌላ በኩልም ኢንተርፕራይዞቹ ይህንን የማምረቻ መሳሪያ በማግኘታቸው ምርታቸው ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ስላስቻለው በገበያው ላይም ከፍተኛ የሆነ ተወዳዳሪ ለመሆን ችለዋል፡፡
ግብርናና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ተመጋጋቢ ለማድረግም በዚህ ዓመት ትስስር ተደርጓል፤ በዚህም የተለያዩ የግብርና ምርቶች በፋብሪካ እየተቀነባበሩና እሴት እየተጨመረባቸው ከቦታ ቦታ ተጓጉዘው እንዲሸጡ በዚህ አምራቹም ገበሬውም እንዲሁም አገር ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝ እየተሰራ መሆኑንም ይገልጻሉ።
መሳሪያው ለኢንተርፕራይዞቹ ከመተላለፉ በፊት አስፈላጊው ትምህርትና ስልጠና ይሰጣቸዋል የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፤ በምን መልኩ አምርተውና አትርፈው ዕዳቸውን መመለስ እንዳለባቸው በቂ ግንዛቤ ስለሚፈጥርላቸውም እስከ አሁን ያለው የብድር አመላለስ 99 በመቶ መሆኑን ይናገራሉ፤ አንዳንዶች ግን በተለይም የገበያ ችግርና የጥሬ እቃ እጥረት የገጥሟቸው ሲሆን፣ በጣም ጥቂቶቹ ደግሞ በቸልተኝነት ዕዳቸውን በፍጥነት ማጠናቀቅ ያለመቻላቸውን አስረድተዋል።
አቶ ወንዳለ ተግዳሮቶች እንዳሉም ይጠቁማሉ፡፡ በተለይም በአመራሩ፣ በህብረተሰቡ እንዲሁም በአንቀሳቃሾቹ በኩል የግንዛቤ ችግር እንዳለ ጠቅሰው፣ ለተጠቃሚዎች መሳሪያ ለመግዛት ሲፈለግ በቂ አቅራቢ ያለማግኘት ችግር መኖሩን ነው የተናገሩት፡፡ የሊዝ ኩባንያዎች እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ብቻ ነው እንዲሰጡ በህጉ የተቀመጠው፡፡ በመሆኑ ከወቅቱ የዶላር ምንዛሪ ጭማሪ ጋር ተያይዞ ችግር እየፈጠረ ነው፤ እነዚህ ነገሮች ደረጃ በደረጃ ማቃለል መቻል ይኖርባቸዋል ይላሉ፡፡
የኦሮሚያ ካፒታል እቃዎች ፋይናንስ ንግድ አክሲዮን ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ መስከረም ደበበ በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ እስከ አሁን ወደ 336 ለሚጠጉ ኢንተርፕራይዞች አንድ ሺ 145 የሚሆኑ ማሽነሪዎችን በብድር ወስደው ወደ ሥራ ይገቡ እንጂ ሥራውን በታሰበው ልክ ሰርተው ጥሩ አፈጻጸም እንዳይኖራቸው የተለያዩ መሰናክሎች ገጥሟቸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በየአካባቢው ማሽነሪዎቹን ለማንቀሳቀስ የሚያስችል የኃይል አቅርቦት አለመኖሩ በጊዜ ማሽነሪዎቹን ተጠቅመው ሥራቸውን ሰርተው በወቅቱ የሚፈለግባቸውን ብድር እንዳይመልሱ አድርጓቸዋል፡፡ጥቂት ቢሆኑም በወሰዱት ማሽነሪ አመርተው ራሳቸውን ለውጠው ዕዳቸውንም በአግባቡ የመለሱ አሉ።
ሥራ ፈላጊዎች ማሽን ብቻ አይደለም የሚያስ ፈልጋቸው፤ መንቀሳቀሻ ገንዘብና የመስሪያ ቦታ እንዲሁም የገበያ ትስስርም ያስፈልጋቸዋል የሚሉት ወይዘሮ መስከረም፤ ከዚህ አኳያ ያሉ ችግሮች በየደረጃው ሊፈቱላቸው እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡ በቀጣይ ግን በታዳጊ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ደረጃ ያሉ የማሽን ፍላጎቶችን በማጥናትና ከአንቀሳቃሾቹ የሚቀርቡትን ፍላጎቶች መሰረት በማድረግ የማቅረብ እቅድ መያዙን ነው የተናገሩት።
የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ እንደሚሉትም፤ በአገሪቱ የኢንዱስትሪ መሰረት ለመጣል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ለዚህ ሽግግር ደግሞ ትልቁ መሰረት የሚሆነው አገራዊ ባለሀብቶችን በብዛት መፍጠር ነው።
የአገሪቱ ምርቶች ከማሳ እንደተሰበሰቡ ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨመርባቸው ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ ሲጓጓዙ ኖረዋል፡፡ይህንን ለመቀየርና እሴት የተጨመ ረባቸው ምርቶችን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ይረዳ ዘንድ የካፒታል ሊዝ ፋይናንስ አገልግሎት ተጀምሯል፡፡
ለአብነትም በአማራ ክልል ላይ ያሉ ወጣቶች እሴት ሳይጨመርበት ለገበያ ይቀርብ የነበረውን የሰሊጥ ምርት አሁን ባገኙት የዘይት መጭመቂያ ማሽን አማካይነት እሴት እየጨመሩ እያቀረቡ መሆናቸውን በማሳያነት ዋና ዳይሬክተሩ ይጠቅሳሉ።
የሊዝ ፋይናንስ አገልግሎቱም የማምረቻ ማሽነሪዎችን የማቅረብ ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅ እንዲሁም አምራቹ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት ይዞ እንዲገኝ ለማድረግ የታሰበ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህ ረገድም ሥራው በተጀመረ በአጭር ዓመታት ውስጥ ትልቅ ተሞክሮዎች መገኘታቸውን ያብራራሉ።
እንደ አቶ አስፋው ገለጻ፤ መንግሥት ሥራው የታሰበውን ያህል ውጤታማ ይሆን ዘንድ በአክሲዮን ማህበራቱ በኩል የሚነሱ የፋይናንስ እጥረቶችን በአፋጣኝ መመለስ ይኖርበታል፡፡ የአቅራቢዎችን ቁጥር ከፍ ማድረግ፣ ከውጭ ለሚመጡት ማሽነሪዎች የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ በበቂ ሁኔታ ማቅረብ፣ በአቅራቢዎች የሚነሱ የጥሬ እቃ አቅርቦቶችንም መፍታት ያስፈልጋል፡፡
«ሌሎች አገሮች በተለይም አደጉ የሚባሉት የሄዱበት መንገድ አሁን እኛ በጅምር እየሄድንበት ያለው መንገድ ነውና አጠናክረን መቀጠል ያሻል፤ አንዳንድ የሚገጥሙ ተግዳሮቶችንም ለመፍታት ቁርጠኛ መሆንና በርብርብ መስራትም ያስፈልጋል» ይላሉ ዋና ዳይሬክተሩ።
በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሊዝ ፋይናንሲንግ ክትትል ዳይሬክቶሬት የቡድን ሥራ አስኪያጅ አቶ የትምጌታ አበራ እንደሚሉትም፤ በመንግሥት ስትራቴጂ የኢንዱስትሪ ልማትን ለማበረታታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ባንኩ የማምረቻ ማሽኖችን ለኢንተርፕራይዞች አቅርቦ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ድጋፍ እያደረገ ነው።
ባንኩ 132 ለሚሆኑ ኢንተርፕራይዞች ማሽነሪዎችን በማቅረቡ በአሁኑ ወቅት ሥራ ጀምረው በማምረት ሂደት ላይ ይገኛሉ። ሌሎቹም ቢሆኑ ማሽነሪ ግዢ እንዲሁም ተከላና ማጓጓዝ ላይ ይገኛሉ፡፡ሁሉም ወደ ሥራ ሲገቡም የሥራ ዕድሉን በመፍጠር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ እንዲሁም አገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመግባት የምታደርገውን ግስጋሴ ያግዛሉ።
ባንኩ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ለሥራው የሚሆን 480 ሚሊዮን ብር ለማሽነሪ ግዢ ወጪ ማድረጉን ገልጸው፤ ይህ ምናልባትም ከእቅዱ አንጻር ዝቅተኛ ሊባል ይችላል በማለት ተናግረዋል፤ ገንዘቡ ዝቅ ሊል የቻለበት ምክንያት የአገር ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ተመን ከፍ በማለቱ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከባንክ የተደረገው የ276 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉ ችግሩን ሊያቃልለው የሚችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ገንዘቡ ደረጃ በደረጃ መለቀቁ ግን በቶሎ ውጤታማ ለመሆን እንደማያስችል አመልክተዋል።
እንደ አቶ የትምጌታ ገለጻ፤ በዚህ ዓመት 12 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር በመለቀቁ በተለይም ከውጭ ለሚገቡት የካፒታል እቃዎች ቅድሚያ በመስጠት ግዥ ተፈጽሟል፡፡ የተገዙትን ወደ ሥራ በማስገባት በቀጣይም በሚለቀቀው ገንዘብ ቶሎ ማሽነሪዎችን በመግዛት ዘርፉን ለማጠናከር ይሰራል፡፡
የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎቱን ባንኩ ብቻውን የሚሰራው ሥራ አይደለም፤ በተለይም ከኤጀንሲው ጋር በቅርበት ይሰራል፡፡ በተያያዘ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በየክልሎቹ 13 ቅርንጫፎችን በመክፈት በየክልል ካሉ ተቋማት ጋር ጥብቅ የሥራ ግንኙነት እንዳለ የሚያስረዱት አቶ የትምጌታ፤ በቀጣይም በቅንጅት ለመስራት መታሰቡንም ተናግረዋል፡፡
በክልልም ይሁን በአዲስ አበባ ያሉት አክሲዮን ማህበራት የተፈቀደላቸው የግዢ ወጪ አንድ ሚሊዮን ብር ነው፤ ልማት ባንክ ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን እስከ 30 ሚሊዮን ብር የመግዛት መብት ያለው በመሆኑ በአክሲዮን ማህበራቱ መስተናገድ ያልቻሉ በባንኩ ሊስተናገዱ ይችላሉ ይላሉ፡፡
እንደ አቶ የትምጌታ ማብራሪያ፤ባንኩ በተቀረጸለት ፖሊሲ መሰረት የሚያስተናግዳቸው የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች አቅም የግድ ከ500 ሺ ብር በላይ ሊሆን ይገባል፡፡በአክሲዮን ማህበራቱም በባንኩም መስተናገድ የማይችሉና በመካከል የሚቀሩ ኢንተርፕራይዞችን ጉዳይም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው ይሰሩበታል።
በተለያዩ ክልሎች የመሰረተ ልማት እንዲሁም የማምረቻ ቦታ ችግር እንዳለ አቶ የትምጌታ ጠቅሰው፣ዋናው ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ችግርና አቅርቦት በሚፈለገው ደረጃ አለመኖሩ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች ኢንተርፕራይዞቹ ወደ ሥራ ሲገቡ ፈተና በመሆን በተገቢው ሁኔታ አምርተው በአግባቡና በጊዜው እዳቸውን መመለስ እንዳይችሉ እያደረጓቸው ነው ይላሉ።ይህም ትኩረት ሊያገኝ የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ነው የተናገሩት።
የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስ ትሪዎችን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር በዚህ መልኩ ለመፍታት መነሳቱን መንግሥት ቢያስታውቅም፣ የመሥሪያ ቦታ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግሮች መሠረታዊ ማነቆዎች መሆናቸው አልቀረም፡፡ እነዚህን ለመፍታት ኤጀንሲው የኢንዱስትሪ ማምረቻ ቦታዎችን ለመገንባት የዲዛይን ሥራዎችን በማከናወን ለክልሎች ማሠራጨቱን መግለጹ ይታወሳል።

እፀገነት አክሊሉ

Published in ኢኮኖሚ

የአሜሪካ የስላለ ድርጅት ሲ አይ ኤ ዳይሬክተር ማይክ ፓምፒዮ በቅርቡ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ቻይና ኢኮኖሚያዊ አቅሟን በመጠቀም ከሩሲያ በበለጠ በአሜሪካውያንና በምእራብ ያውያን ላይ ተፅእኖ እየፈጠረች ነው ሲሉ ገልጸው ነበር ፡፡ ቻይና የተለያዩ ሽፋኖችን በመጠቀም የአሜሪካን የንግድ መረጃዎች ለመስረቅ እያነፈነፈች መሆኗን በመጠቆም እንጠንቀቅ ሲሉም ዳይሬክተሩ ተደምጠዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ሮይተርስ ከቤጂንግ እንደዘገበው፤ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቴለርሰን የላቲን አሜሪካ ሃገራት ከቻይና ጋር የሚያደርጉትን ቅጥ ያጣ የኢኮኖሚ ቁርኝት እንዲቆም ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን ተከትሎ ቻይና አሜሪካን እየከሰሰች ነው፡፡
ሬክስ ቴለርሰን የላቲን አሜሪካ ሃገራት ሜክሲኮ፣አርጀንቲና፣ፔሩ፣ኮሎምቢያና ጃማይካን ከመጎብኘታቸው በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ቻይና በላቲን አሜሪካ ሃገራት ላይ ኢኮኖሚያዊ አቅሟን በመጠቀም ቀጣናውን በራሷ ምህዋር ውስጥ ለመክተት እግሯን እያስገባች ነው ብለዋል፡፡
ባለፈው አርብ ቴለርሰን የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ ተከትሎም የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው፣ በቻይናና በላቲን አሜሪካ ሃገራት መካከል ያለው ትብብር በጋራ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የተባለው ከእውነት የራቀና ብዙሃኑን የላቲን አሜሪካ ሃገራት ያላከበረ ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
የቻይናና የላቲን አሜሪካ ሃገራት ትብብር በእኩልነት፣ በአጋርነት፣በግልፅነትና በሁሉን አቀፍ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ሚኒስትሩ ጠቅሰው፤ ቻይና ዋነኛ የላቲን አሜሪካ እቃዎችን እና እሴት የተጨመረባቸውን የግብርና ምርቶች በብዛት ወደ ሀገሯ የምታስገባ ሀገር መሆኗንም አመልክተዋል፡፡
ቻይና ከላቲን አሜሪካ ሃገራት ጋር ያላት ኢንቨስትመንትና የፋይናንስ ትብብር በንግድ እና በአካባቢ ህግና ደንቦች የሚመራ መሆኑንም ነው ሚኒስትሩ የጠቀሱት፡፡ እያደገ የመጣው የቻይናና የላቲን አሜሪካ ግንኙነት ሶስተኛ ወገንን ለመጨፍለቅ ያለመ አይደለም ብለዋል ፡፡ አብዛኛዎቹ ሃገራት ኋላ ቀር የዜሮ ድምር ጨዋታን ወደጎን በመተው ግልፅና ሁሉን ባካተተ መልኩ እያደገ ወደመጣው የቻይና ላቲን አሜሪካ ግንኙነት እንደሚመለከቱ ተስፋ አለኝ ሲሉም ገልፀዋል፡፡
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ ባለፈው ወር ቺሊን መጎብኘታቸው የሚታወስ ሲሆን በላቲን አሜሪካና ካሪቢያን ሃገራት ጉባኤ ላይ በመገኘት ከጉብኝታቸው ጎን ለጎን ቺሊያውያን ግዙፍ በሆነው የቻይና የመንገድ ልማት ፕሮግራም ተሳታፊ እንዲሆኑ ጋብዘዋቸዋል፡፡
የአሜሪካን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዲፕሎማት ዴቪድ ማልፓስ በበኩላቸው ቻይና የፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮን ሶሻሊስታዊ መንግስት መረማመጃ በማድረግ ደካማውን የቬንዝዌላ አስተዳደር እያነቃች ነው በሚል እየከሰሱ እንደሚገኙም ነው የሮይተርስ ዘገባ ያስረዳው፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

Published in ዓለም አቀፍ

የሩቅ ምስራቅ እስያዋ ትንሿ ሀገር ሰሜን ኮሪያ በኑክሌር ማበልጸግ እና በተደጋጋሚ በምታደርጋቸው የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳይል ሙከራዎቿ የአለም ስጋት ሆናለች፡፡ በተለይ ይህን ተግባሯን በጽኑ በመቃወም ላይ በምትገኘው አሜሪካ ላይ ከሚሳይል ባልተናነሰ መልኩ የምታወርዳቸው ዛቻዎች በየእለቱ እየጨመሩ መጥተዋል፡፡
ሃገሪቷ ከዚህ ድርጊቷ እንድትቆጠብና የተበባሩት መንግስታት ድርጅት፣ አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት በተደጋጋሚ ማእቀቦችን ሲጥሉባት ቆይተዋል፡፡ በቅርቡ እንኳ በውጭ ሃገር የሚሰሩ ዜጎቿ ወደሃገራቸው የሚልኩትን ገንዘብ እንዲያቆሙና ወደ ሃገሪቱ በሚገባው የተጣራ ነዳጅ ላይ የተባበሩት መንግስታት ማእቀብ መጣሉ ይታወሳል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት በአሜሪካና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሀገሪቱ ላይ የተጣሉ ማእቀቦች በዋናነት የተለያዩ እቃዎች ወደ ሀገሪቱ ድርሽ እንዳይሉ የሚከለክሉ ሲሆን፣ወደ ውጪ በምትልካቸው ምርቶች ላይ የተጣለው ማእቀብም እንደ ጸና መሆኑ ይታወቃል፡፡
ይሁንና ማን አይዞሽ እንዳላት ባይታወቅም ሀገሪቱ አሁንም ማእቀቡን በመጣስ የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጭ መላኳን ቀጥላበታለች፡፡ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ቢቢሲ ይዞት የወጣው መረጃ እንዳመለከተው ሰሜን ኮሪያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ወደ ውጪ እቃዎችን እንዳትልክ የጣለባትን ማእቀብ በመተላለፍ በአንድ አመት ውስጥ ብቻ 200 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኝት ችላለች፡፡
ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተውጣጣው የባለሙያዎች ቡድን ሰሞኑን ያቀረበው ሪፖርት እንዳመለከተው፤ቻይና፣ሩሲያና ማሌዢያን የመሳሰሉ በርካታ ሃገራት በማእቀቡ የታሰረውን የሰሜን ኮሪያን ህገወጥ የወጪ ንግድ አላቆሙም፡፡ ዋነኛ ተቀባዮቹም እነዚሁ ሃገራት ናቸው፡፡
ከንግድ ልውውጡም በተጨማሪ ሃገሪቷ ከሶሪያና ማይናማር ጋር የባልስቲክ ሚሳይል ትብብር እያደረገች መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ቀደም ሲልም እኤአ ከ2012 እስከ 2017 ድረስ ከ40 በላይ የመርከብ ጭነት ወደ ሶሪያ መጓጓዙን ሪፖርቱ ጠቁሞ ፣ይህም ለሶሪያ የሳይንስና ምርምር ማእከል ለሚያካሂደው የኬሚካል ጦር መሳሪያ መርሀ ግብር የሚውል መሆኑንም አስታውቋል፡፡
በባለሙያዎቹ ቡድን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የቀረበው ይኸው ሪፖርት እንደጠቆመው፤ ሰሜን ኮሪያ እቃዎችን ወደ ውጪ እንዳትልክ የሚከለክለውን ውሳኔ በመተላለፍ ከጥር ወር አንስቶ እስከ መስከረም 2017 ባለው ጊዜ የወጪ ንግዱን አጧጡፋለች፡፡ ሪፖርቱ ጨምሮ እንደሚያሳየው በርካታ በስም የማይታወቁ ትላልቅ የነዳጅ ኩባንያዎችም ጭምር ለሰሜን ኮሪያ የነዳጅ ምርቶችን በህገወጥ መንገድ በማቅረብ ሃገሪቷ ላይ የተጣለባትን ማእቀብ በመተላለፋቸው ምርምራ እየተካሄደባቸው ይገኛል፡፡
በመርከብ የተጫነ በርካታ የድንጋይ ከሰል ማእድን በተለያየ ጊዚያት የተለያዩ የማጭበርበር ዘዴዎችን በመጠቀምና የመዳረሻ መስመሮችን በመቀያየር ወደ ቻይና ፣ማሌዢያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ሩሲያና ቬትናም እንዲገባ ተደርጓል፡፡ይህም ሰሜን ኮሪያ ከእነዚህ ሃገራት ጋር በህገወጥ መንገድ የንግድ ሸሪክ መሆኗን ይጠቁማል፡፡
ማይናማርና ሶሪያ ማዕቀብ ከተጣለባቸው ሃገራት ጥቁር መዝገብ ውስጥ የተካተቱ ቢሆኑም፣ የተባበሩት መንግስታት ተቆጣጣሪ ቡድን ከሰሜን ኮሪያ ዋነኛ የጦር መሳሪያ ላኪ የኮሪያ ማእድንና ልማት ንግድ ትብብር ጋር ያላቸውን ትብብር መቀጠላቸውን ደርሼበታለው ሲልም ገልጿል፡፡ ሀገሪቱ የነዳጅና ነዳጅ ውጤቶችን ማእቀብ ጥሰት ያደረገችው ከመርከብ ወደ መርከብ በመገልበጥ ሲሆን ይህ የሚፈጸመውም በቻይናዋ ታይዋን ግዛት እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
የሶሪያ ባለስልጣናት በሶሪያ የሚገኙት የሰሜን ኮሪያ ባለሙያዎች የስፖርት ተሳታፊ ናቸው ሲሉ ጉዳዩን በማስተባበል ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቆጣጣሪ ቡድን አስታውቀዋል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የማይናማር አምባሳደር በበኩላቸው ከሰሜን ኮሪያ ጋር ምንም አይነት የጦር መሳሪያ ግንኙንት የለንም ሲሉ ገልፀዋል፡፡
በኮሪያ ልሳነ ምድር በሰሜንና ደቡብ ኮሪያ መካከል ያለው ወታደራዊ ውጥረት እስከቅርብ ጊዜ ድረስ መቀጠሉ ይታወቃል፡፡ በደቡብ ኮሪያውያን በኩል ሰሜን ኮሪያዎች በክረምት ኦሎምፒክ ስፖርት ተሳታፊ እንዲሆኑ የቀረበው ግብዣ ተቀባይነት ማግኘቱ ይህን በሁለቱ አገራት መካከል አዲስ ግንኙነት ለመጀመር መልካም አጋጣሚ ነው ሲሉ በርካታ ወገኖች እየገለጹ ናቸው፡፡ በቅርቡም የሰሜን ኮሪያ ልኡካን ቡድን ወደ ደቡብ ኮሪያ እንደሚያቀና ይጠበቃል፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

Published in ዓለም አቀፍ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።