Items filtered by date: Wednesday, 07 February 2018
Wednesday, 07 February 2018 18:12

«የእኛ ህይወት»

ገና የሁለት አመት ህጻን ሳለች ነበር እናት አባቷ በፍቺ የተለያዩት ።የወላጆችዋ እህል ውሀ  እንዳበቃ የእሷና የወንድሟ ዕጣ ፈንታ ሊወሰን ግድ ሆነ ። ከንብረት ክፍፍሉ  በኋላ ወንድሟን የእናቱ እናት ተረከቡት። እሷ ደግሞ ለአባቷ እናት ተሰጠች። ከዚህ በኋላ የብርቄ ንጋቱ የልጅነት ህይወት በፈተና የተሞላ ሆነ።
 የህጻኗ ብርቄ በአያቷ ቤት ድንገት መቀላቀል አክስት አጎቶችዋን አላስደሰተም። የእሷ መምጣት ከሀብትና ከውርስ ጋር ተያይዞ ሁሉም በጥላቻና በጥርጣሬ ያስተውሏት ጀምሯል። ቤተሰቡ  እንደልጅነቷ አያስብላትም።  የለበሰችው በላይዋ አልቆ ተርባ ውላ ስታድርም ግድ የሚሰጠው አልነበረም።ታማ ስትተኛና ተሽሏት ስትነሳም ምን ሆንሽ? የሚላት አልተገኘም። አያቷ ለመሬት ሙግት ደብረሲናን ተሻግረው አዲስ አበባ መክረማቸው ደግሞ የትንሿን ብርቄ አስተዳደግ ይበልጥ ያሳሳው ጀመር።
 ዘመዶችዋ የአያቷን በቤት አለመኖር ሲያዩ በገመድ አስረው ያሳድሯታል። እየገረፉና እያስፈራሩም ውርስ ማግኘት እንደማትችል ይነግሯታል። የዚህ ትርጉም የማይገባት ጨቅላ ዱላና ማስፈራሪያቸውን  በእሽታ ትቀበላለች።  ዕንባና ሲቃዋን ውጣም የሚሏትን  ሁሉ ትችላለች ።አሁን የትም መሄድ አይቻላትም። የእናትዋ ዘመዶች ቢያገኟት ልብሷን አውልቀውና ከበርሜል ከተው እንደሚበሏት ነግረዋታል።
ይህን የሰማችው የአምስት አመት ህጻን የተባለችውን አምና ተቀብላለች። የእናቷ ወገኖች አብረዋት ካሉት አጎቶችዋ ይበልጥ ክፉ መሆናቸውን የልጅነት አዕምሮዋ ነግሯታል። በዚህ መሀል ሊያያትና ሊጠይቃት የሚመጣ ጸጉረ ልውጥ ሁሉ ለእሷ በጠላትነት ተፈርጇል። እነሱ እንዳሏት በእናቷ ዘመዶች መበላትን አትፈልግም። ስለዚህ ከመሸሽ ውጭ ምርጫ አልነበራትም።
 ብርቄ ሁሌም የሚደርስባት ችግርና ረሀብ ከጉስቁልናዋ ጋር ተዳምሮ ሰውነቷን አገረጣው። እያደር በገጽታዋ መታየት የጀመረው ሽፍታ ደግሞ መልኳን ቀይሮ ማንነቷን ለወጠው። ይህን ያዩ አያቷ ምልክቱ ከጭርት እንደማያልፍ ገምተው የብሳና ቅጠል  እየበጠሱ አሻሽተው ሊያድኗት ሞከሩ። ውሎ ሲያድር ግን ቁስሉ ከመጥፋት ይልቅ  ተባባሰ  ።እብጠትና ስፋት ጨምሮም መላ ሰውነቷን አዳረሰ ።
ይሄኔ አያት ሙከራቸው እንዳልሰመረ  ገባቸው። መድህን ላሉት መፍትሄም ጠበል ወስደው ሲያስጠምቋት ቆዩ። አሁንም ግን ህመሙ ከመዳን ይልቅ እየባሰበት ሄደ።    አያት ቆም ብለው አሰቡ። የሀሳባቸው ጫፍም ከሆስፒታል ደጅ አድርሶ ታማሚዋን  ለህክምና አበቃ። ከሀኪሞቹ እጅ የደረሰችው ትንሿ ብርቄ ለማስታገሻ አንድ መርፌ  ተወግታ ከማረፊያው እንደተቀመጠች አያት ቀጣዩ ህክምና እስኪደርስ  እሷን  ትተው ወደ ውጭ ወጣ ሊሉ አሰቡ።
    ይህ በሆነ አፍታም አንዲት ሴት ወደእሷ ቀረበች። የሰውነቷ መቀየር፣ በቁስል መሸፈንና የልብሷ እጅግ መቆሸሽ አስደንግጧታል። የምታያት ልጅ የቅርብ ዘመዷ መሆኗን  እንዳወቀች  ጠጋ ብላ  በስሟ ጠራቻት።ብርቄም ማንነቷ አልጠፋትም። የእናቷ ቤተሰብ መሆኗ ግን ወደእሷ እንዳትፈጥን አገዳት። እነሱ ቀቅለው  እንደሚበሏት  ሲነገራት የኖረው ትውስ ቢላት ልትሸሻት ሞከረች።
ሴትዬዋ ግን  በቀላሉ ልትተዋት አልፈለገችም። እንደምንም አግባብታና አሳምና አዲስ አበባ እናቷ ቤት አደረሰቻት። ብርቄ ህይወትን በአዲስ መልክ ስትጀምር ውስጧ በደስታ ተሞላ ።ለአመታት ስትናፍቃት የኖረችው እናቷን በማየቷም ከልቧ ተደሰተች። ይህ ደስታ ግን እምብዛም አልዘለቀም። ከእናቷ ጋር የሚኖረው እንጀራ አባት በክፉ አይን ያያት ጀመር።
የህመሟ መባባስ ሲጨምር እናት በየሆስፒታሉ ይዘዋት ተንከራተቱ። ሆኖም ችግሩ በቀላሉ ተለይቶ መፍትሄ ሳይገኝለት ቆየ ።አንድቀን ግን ቀድሞ «ቦርቸሌ»ይባል ከነበረ ስፍራ እናትና ልጅ  ደረሱ። በወቅቱ በስፍራው የነበረች አንዲት የውጭ ዜጋ ሀኪምም በአይኗ ብቻ አይታ የበሽታው  መፍትሄ  ያለው ዘነበወርቅ ሆስፒታል  መሆኑን ጠቆመቻቸው።
ብርቄና እናቷ ከሆስፒታሉ ደጃፍ ሲደርሱ በርካታ የስጋደዌ ተጠቂዎችን  ተመለከቱ። እናት ይህን ሲያስተውሉ ወደ ልጃቸው ዞረው መጮህ  ጀመሩ ። ከየት አመጣሽው በሚል ንዴትም ያዋክቧት ያዙ። የሚሉት ሁሉ ያልገባት ብርቄ በነገሩ ብትደናገጥም የምርመራው ውጤት የስጋደዌ ተጠቂ መሆኗን አመላከተ።
ከዚህ በኋላ እናት በድንጋጤ ታመው አልጋ ያዙ። የሰሙትን ባለማመንም ብርቄን አዋቂ ዘንድ ይዞ ለመሄድ ወሰኑ። አሁን የስድስት አመቷ ህጻን አዋቂ ከተባለው ሰው ቤት አገልጋይ እንድትሆን ተፈርዶባታል። የእናቷን ፍቅር በወጉ ያልጠገበችው ልጅ ከአቅሟ በላይ የተጫነባትን ሀላፊነት መቋቋም አልቻለችም። እንደታሰበው ከበሽታዋ  አልተፈወሰችም። ይልቁኑም እጅና እግሮችዋ ስሜት አልባ ሆነው መደንዘዝ ጀመሩ።
ብርቄ በህመሟ ምክንያት የቀረበላትን እንጀራ በወጉ መጉረስ አልተቻላትም።ይህ እውነታ ደግሞ ከቤቱ ሰው ጋር የሚያስማማት አልሆነም። የምታደርገው ሁሉ በሆስፒታሉ እንዳየቻቸው ሰዎች ለመሆን የሚመስላቸው እናቷና የእንጀራ አባቷ ሁሌም ይቃወሟታል። እሷ ግን በመላው ስውነቷ ቁስልና በደረሰባት የከፋ ህመም እየተሰቃየች ነበር።
ዕድሜዋ አስር አመት ሲሞላው ለራሷ መቆም እንዳለባት አሰበች። ህክምናውን ለመጀመር ስትወስንም ሀሳቧን ደግፈው በርካቶች ከጎኗ  ቆሙ። በሆስፒታሉ ደርሳ አልጋ ስትይዝ ግን እጆችዋና ሁለት እግሮችዋ እጅግ ተጎድተው ነበር። ዛሬ ይህ ታሪክ ካለፈ በርካታ አመታት ተቆጥረዋል። አሁንም ግን ወይዘሮ ብርቄ በወቅቱ ህክምናውን ያለማግኘቷን አጋጣሚ ስታስታውስ እጅግ ይቆጫታል።ይሁን እንጂ እነዛ አስቸጋሪ የህይወት መስመሮች ለዛሬ ማንነቷ ብርታት ሆኗታል።
አሁን በአራት ልጆችዋና በሶስት የልጅ ልጆችዋ ወግና ማዕረግ ከመኩራት በዘለለ እንደሷ የስጋ ደዌ ተጠቂ ለሆኑ ወገኖች ያላትን አጋርነት ለማሳየት ሌት ተቀን ትለፋለች።መስራት፣ መለወጥና መማር እንደሚቻል በማወቋም ለነገ የተሻለ ህይወት መሰረት በሆናት የዕደ ጥበባት ማምረቻ ውጤት ላይ ተሳታፊነቷን በተግባር እያሳየች ነው።
አቶ ቸሩ ገብሬ ተወልደው ካደጉበት ቀዬ ርቀው አዲስ አበባ ለመገኘት ያስገደዳቸው በድንገት ያጋጠማቸው የስጋ ደዌ ህመም ነበር። የዛኔ ገና የአስራ ሁለት አመት ልጅ ነበሩ። በወቅቱ በፊታቸው ላይ የተከሰተው ነጭ ምልክት የስጋ ደዌ  መሆኑን የጠረጠሩ ወላጆቻቸው የመጀመሪያ ምርጫቸው ባህላዊ መድሀኒት ነበርና እሱን ሲከታተሉ ቆዩ ።ይሁን እንጂ ይህ አማራጭ ዘላቂ መፍትሄ ባለመሆኑ አዲስ አበባ የቀድሞው ዘነበወርቅ ሆስፒታል እንዲመጡ ግድ ነበር።
ከአባታቸው ጋር አዲስ አበባ የመጡት አቶ ቸሬ ተመልሰው አገራቸው አልገቡም። ህመሙ ተባብሶ የከፋ ችግር እንዳያስከትልም በተከታታይ መታከማቸውን አላቆሙም።ያረፉበት የዘነበወርቅ አካባቢ የስጋደዌ  ተጠቂዎች  መኖሪያ  መሆኑ ለእሳቸው መልካም አጋጣሚ ነበር። አንዳንዴ ግን ወደ ከተማ መዝለቅ ሲፈልጉ የነበረውን መገለል አይዘነጉትም። በተለይ ሰባት ቁጥር የከተማ አንበሳ አውቶቡስን ሰዎች ከተጠቂዎቹ ጋር አዛምደው ያስቧት እንደነበር ያስታውሳሉ።
በወቅቱ የኔ የሚሉት ዘመድ ያልነበራቸው አቶ ቸሬ የሊስትሮ ዕቃ ገዝተው ጫማ ማሳመር መጀመራቸው  ከብዙ ሰዎች ጋር የመግባባት አጋጣሚን ፈጠረላቸው ።በነበራቸው ትርፍ ሰአት ከአቻዎቻቸው ጋር መማራቸው ደግሞ ይበልጥ ቀረቤታን ፈጥሮ ከመገለል ታደጋቸው። በተለይ የዘነበወርቅ ነዋሪዎችና የበሽታው ተጠቂዎች በአብሮነት የፈጠሩት ማህበራዊነት ይበልጥ ሌሎችን እንዲቀርቡ አደረገ። ይህ መልካም አጋጣሚ ግን በቀላሉ የተፈጠረ አልነበረም። እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች መሰሎቻቸው በተጎዳው አካላቸው ምክንያት በርካታ ፈተናዎችን አሳልፈዋል።
የስጋደዌ ተጠቂዎቹም  ቢሆን የሚደርስባቸውን  መገለል  አምነው የተቀበሉበት እውነታ እንደነበር አቶ ቸሬ ያስታውሳሉ። በወቅቱ የደርግ መንግስት በአፈሳ መልክ ወደ መጠለያ እንዲገቡ ባደረገበት አጋጣሚ  ትምህርታቸውን ለመቀጠል ምክንያት ሆኖ እስከ አስረኛ ክፍል ለመማር ቻሉ። ከመጠለያው ከወጡ በኋላም ራሳቸውን ለማስተዳደር  የጀመሩት የቀን ስራ ለገቢያቸው መጨመር ምክንያት ሆኖ እስከ ንግድ ስራ አደረሳቸው።
የዛሬ ሀያ ስድስት አመት ትዳር ለመያዝ ሲያስቡ እጮኛቸው የህመሙ ተጠቂ አልነበረችም። የአሳዳጊ አያቷ በጎ አመለካከት እንደሌሎች ጋብቻውን ለማደናቀፍ ምክንያት አልሆነም። ዛሬ አቶ ቸሩና መሰሎቻቸው የአዲስ አበባ ስጋደዌ ተጠቂዎች ማህበርን አቋቁመው በርካታ ተግባራትን እያከናወኑ ነው። ልጆቻቸውን በማስተማር ያገኙትን ውጤታማነትና በትዳራቸው ያላቸውን ደስታ የሚገልጹት በታላቅ ኩራት ነው።
ከተወለዱት አስራ ሁለት ልጆች መሀል በአንዷ ላይ ብቻ የታየው የስጋ ደዌ ምልክት መላው ቤተሰብን የሚያስደነግጥ ነበር። ይህ መሆኑ ደግሞ ክብነሽ ተማም ላጋጠማት ችግር የአዋቂ ተብዬዎችን እጅ እንድትናፍቅ ምክንያት ሆኖ ቆየ። የግንዛቤ ማነስ የፈጠረው ክፍተትም  ህክምና ሳታገኝ በስቃይ እንድትንገላታ አደረጋት።
ልጅነቷን በስቃይ የገፋችው ህጻን ዘግይቶም ቢሆን አዲስ አበባ ለህክምና ደረሰች ።ይሁን እንጂ  የወሰደችው ቆይታ ለጉዳት በመዳረጉ እግሯ እንዲቆረጥና በሰው ሰራሽ አካል እንዲተካ ተደረገ። ዛሬ ክብነሽ የአንዲት ሴት ልጅ እናት ሆናለች። ቤተሰቧን ለመደጎምም ጥንካሬን ተላብሳ ስራ ውላ መግባትን ለምዳለች።
ዘንድሮ በሀገራችን ለ19ኛ ጊዜ የተከበረው ዓለም አቀፍ የስጋደዌ ቀን «የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ስጋ ደዌን ለማጥፋት በጋራ እንስራ» የሚል መርህን አንግቧል። የኢትዮጵያ ስጋ ደዌ ተጠቂዎች ብሄራዊ ማህበር በሰባት ክልሎችና በ68 ቅርንጫፍ ማህበራት የታቀፈ ነው። የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጫንያለው ህብስቱ እንደሚሉት ማህበሩ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ እየተንቀሳቀሰ ነው። በቅርቡም የትምህርትና የስልጠና ማዕከልን ለማስገንባት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሊዝ ነጻ ያገኘውን  መሬት ተረክቦ የመሰረት ድንጋይ ለመጣል ችሏል።
ባለፈው ሳምንት ቀኑን አስመልክቶ በተካሄደው ውይይት የኢትዮጵያ ስጋደዌ ተጠቂዎች ብሄራዊ ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ታደሰ እንዳሉት ካለው የግንዛቤ እጥረት የተነሳ በሀገራችን የስጋ ደዌ ህሙማን ቁጥር እየጨመረ ይገኛል።በዚህም ምክንያት የአካል ጉዳተኞች ቁጥር በመበራከት ላይ ነው። ይህን ችግር ለመቅረፍም የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማስፋት ግድ ይላል።
የስጋ ደዌ ተጠቂዎቹ ያለፉበትን ከባድ የህይወት ውጣ ውረድ ለሌሎቹ በማካፈል ችግሩን ለመከላከልና መገለልን ለማስቀረት የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ ህይወታችን ይህን ይመስላል በማለትም ምስክርነታቸውን በአደባባይ እየሰጡ ነው፡፡ በተለይም የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ግንባር ቀደም ተሳታፊ እየሆኑ ነው፡፡
አለምአቀፉን የስጋደዌ ተጠቂዎችን ቀን ለማክበር በሳፋሪ አዲስ ሆቴል በተደረገው ስነስርአት በአቶ ደሳለኝ ተሬቻ በእንግሊዝኛ ተጽፎ በደራሲ የዝና ወርቁ ወደ አማርኛ የተመለሰው ‹‹አቅመቢስ አሸባሪው›› የተሰኘው መጽሀፍ ለምርቃት በቅቷል። መጽሀፉን በራሷ በጎ ፈቃደኝነት ተነሳስታ ለንባብ ያበቃችው ደራሲ የዝና ወርቁ ለማህበሩ በነጻ አስረክባለች። መጽሀፉ የስጋደዌ ተጠቂዎችን ህያው ምስክርነት የያዘ ሲሆን በዚህ ህይወት ውስጥ ያለፉ ሰዎች ልምድና ተሞክሯቸውን ያካፈሉበት መዘክር መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።

 

Published in ማህበራዊ
Wednesday, 07 February 2018 17:23

አዲስ ዘመን ዛሬ

በአዲስ አበባ ከተማ ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አካባቢ ነው የተወለዱት። ከ1958 ዓ.ም እስከ 2009 ዓ.ም ከተጫዋችነት እስከ አሠልጣኝነት ባለው የእግር ኳስ ህይወት ውስጥ አልፈዋል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያዎች በብሄራዊ ቡድን በተከላካይ ስፍራ ላይ በመጫወት ለአገራቸው የበኩላቸውን ተወጥተዋል፡፡ በክለብ ደረጃም ዳርማር ከተሰኘው የሰፈር ክለብ እስከ አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ የዘለቀ የተጫዋችነት ህይወትን አሳልፈዋል-አንጋፋው የስፖርት ሰው አስራት ኃይሌ።
ለ50 ዓመታት የሚዘልቀው የአስራት ኃይሌ የስፖርት ጉዞ ከተጫዋችነት ወደ አሠልጣኝነት ሙያ በመግባት በአገሪቱ የሚገኙ አሠልጣኞች በሙያው ሊደርሱበት ያልቻሉትን የውጤት ታሪክ መሥራት ችለዋል፡፡ በአሠልጣኝነት ዘመናቸው ከ36 ያላነሱ የተለያዩ ዋንጫዎችን በማንሳት አቻ ያልተገኘለትን ታሪክ በደማቅ ቀለም ፅፈዋል። አንጋፋው አሠልጣኝ ከተጫዋችነት እስከ አሠልጣኝነት፤ ከክለብ እስከ ብሄራዊ ቡድን ድረስ ያሳለፈውን ጉዞ፣ ያካበተውን ልምድና በአገሪቱ የእግር ኳስ እንቅስቃሴ እና በተያያዥ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ ዘመን የስፖርት ዝግጅት ክፍል ያደረገው ቆይታ እንዲህ ይቀርባል።
አዲስ ዘመን:- ከዳርማር እስከ ቅዱስ ጊዮርጊስ የዘለቀው የተጫዋችነት ጊዜዎት ምን ይመስል እንደነበር በማስታወስ ጭውውታችንን ብንጀምር?
አሠልጣኝ አስራት:- የእግር ኳስ ጉዞዬ የሚጀምረው በ19 58 ዓ.ም ነው። የ13 ዓመት ልጅ እያለሁ ዳርማር በሚባል የሰፈር ክለብ። በዚህ ክለብ ውስጥ ከሲ እስከ ቢ ከዛም ኤ ባለው ደረጃ ተጫውቻለሁ። በእግር ኳሱ ራሴን እያሳደኩኝ እና አቅሜን እንዳጎለብት አቅም ፈጥሮልኛል፡፡ በ1962 ዓ.ም መጨረሻ ላይም ወደ ድሬዳዋ በማቅናት ጥጥ ማህበር መጫወት ጀመርኩ። ከጥጥ ማህበር ጋር በነበረኝ የስምንት ዓመት ቆይታ ጥሩ ጊዜ አሳልፌአለሁ። የሚገርመው ክለቡን በተቀላቀልኩ በመጀመሪያው ዓመት ላይ ነበር ለብሄራዊ ቡድን የተመረጥኩት። ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ በመምጣትም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በርካታ ዓመታትን አሳለፍኩኝ ። ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና በኋላም በአዲሱ የደርግ ክለቦች አደረጃጀት በትግል ፍሬ ክለብ ውስጥ በተጫዋችነት አሳልፌያለሁ። በነበረኝ እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ ለብሄራዊ ቡድን የመጫወት ዕድሉን ለማግኘት ችያለሁ።
አዲስ ዘመን:- በተጫዋችነት ጊዜዎት በብሄራዊ ቡድን የመጫወቱ አጋጣሚው ምን ያህል ነበር?
አሠልጣኝ አስራት:-በብሄራዊ ቡድን ደረጃ የመጫወት አጋጣሚውን በተለያየ ጊዜያት አግኝቻለሁ። በ10 የአፍሪካ ዋንጫ እና ለ11 ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያዎች ላይ በመመረጥ ተጫውቻለሁ።
አዲስ ዘመን: - ከብሄራዊ ቡድን ራስዎትን ሲያገሉ፤ በክለብ ደረጃ ይጫወቱ ነበር። ከብሄራዊ ቡድን ለማግለል ከውሳኔ ያደረሰዎት ምንድን ነው?
አሠልጣኝ አስራት:- ከብሄራዊ ቡድን ራሴን ለማግለል ምክንያት የነበረው ለ11ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከኡጋንዳ ከነበረን ጨዋታ ታሪክ ጋር ይገናኛል። በወቅቱ ብሄራዊ ቡድኑ ማጣሪያውን ወደ ኡጋንዳ በመጓዝ አከናውኗል። በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ለማሸነፍ ጥረት አደረግን። በአጋጣሚ በጨዋታው ላይ በተፈጸመብኝ ጥፋት ተጎዳሁ። ተቀይሬ ለመውጣት ተገደድኩኝ። ቡድናችን ጥሩ እንቅስቃሴ ቢያደርግም በመጨረሻው ሰዓት በተቆጠረብን ግብ ተሸንፈን ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ሳንችል ቀረን። ከኡጋንዳ መልስ የቡድን መሪዎቹም እና ሌሎች ከቡድኑ ጋር የተጓዙት አመራሮች ብሄራዊ ቡድኑ ሆን ብሎ ነው የተሸነፈው የሚል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጡ።
በቡድን መሪዎቹ የተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ስህተት እንደሆነ እና ሆን ብለን አለመሸነፋችንን ለመናገር አንደኛና ሁለተኛው የቡድኑ አምበሎች ቃለ መጠየቅ አልሰጡም። ጉዳዩን ወደ ፖለቲካ ቀይረው ፀረ አብዮት አልያም ቀይሽብር የሚል መዘዝ እንዳያመጣ በመፍራት ዝምታን መረጡ። የቡድኑ ሦስተኛ አምበል እኔ እንደመሆኔ ጥያቄው ወደ እኔ ተሻገረ፤ እውነቱ መታወቅ ስላለበት ሆን ብለን እንዳልተሸነፍን፤ ለማሸነፍ ብንጥርም ሳይሳካ መቅረቱን ከተወሰኑ ተጫዋቾች ጋር በመሆን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠን፡፡ ፍፁም ቅጣት ምት ብናገኝም ማስቆጠር አልቻልንም ። ግቡም የተቆጠረብን በዳኛው ስህተት ነው።
በወቅቱ ዳኛው ማጫወት ከነበረበት ሰዓት ያለ አግባብ አምስት ደቂቃ ጨመረ። በጭማሬው ሦስተኛ ደቂቃ ነው ኡጋንዳዎች ግብ ያስቆጠሩት። ግቡ እንደተቆጠረ ዳኛው ጨዋታው ተጠናቋል ሲል ፊሽካውን አንጫረረ። በዚህም በሜዳችን 1ለ1 ተለያይተን ስለነበረ ሳናልፍ ቀረን። በመግለጫው ይህን ተናገርን። ብሄራዊ ቡድኑ ለሌላ ጨዋታ ሲሰባሰብ ወደ ቡድኑ ለመቀላቀል በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተሳተፋችሁ ተጫዋቾች የይቅርታ ደብዳቤ ካልጻፋችሁ አትካተቱም ተባልን። ከእኔ ጋር የነበሩት ተጫዋቾች የይቅርታ ደብዳቤ ሲያስገቡ እኔ ግን አሻፈረኝ አልኩኝ። ምክንያቱም ባልፈጸምኩት ጥፋት ተጠያቂ መሆን ስለሌለብኝ ።ይሄንን ተከትሎ ሳልፈልግ ከብሄራዊ ቡድን ተጫዋችነት ራሴን አገለልኩ። በወቅቱም ለቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ እጫወት ነበር። ከዛም ወደ አሠልጣኝነት ህይወት ተሸጋገርኩኝ።
አዲስ ዘመን:- ከተጫዋችነት ህይወት ሳይወጡ ነው ወደ አሠልጣኝነት የገቡት የዚህን ጅማሮና ጉዞውን በአጭሩ ቢያስረዱን?
አሠልጣኝ አስራት:- እውነት ነው፤ ወደ አሠልጣኝነት ሙያው የገባሁት ተጫዋች እያለሁ ነው። የመጀመሪያ ክለቤም ህንፃ ኮንስትራክሽን ነው፡፡ በወቅቱ 50 ቡድኖች ሲዋቀሩ ህንፃ በአዲስ መልክ ተመሠረተ፡፡ በውድድሩ ባስመዘገበው ጥሩ ውጤት ምርጥ 10 ውስጥ በመግባት ከሁለተኛ ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን አለፈ፡፡ በወቅቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፈርሶ ነበር፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደ አዲስ ተቋቁሞ ክለቡን ወደ ላይኛው ዲቪዚዮ እንዲገባ በሚደረገው ጥረት እኔም አስተዋጽኦ ለማድረግ እንድጫወት ጥሪ ቀረበልኝ። በመሆኑም ለቅዱስ ጊዮርጊስ እየተጫወትኩኝ፤ ህንፃ ኮንስትራክሽን አሠለጥን ነበር። ይሁንና ጊዮርጊስ በመጨረሻው ጨዋታ በመድን ተሸንፎ ጥረታችን ሳይሳካ ቀረ። እኔም ሙሉ ጊዜዬን ከተጫዋችነት ወደ አሠልጣኝ በማሸጋገር ከህንፃ ኮንስትራክሽን ጋር ጉዞዬን ቀጠልኩኝ። ህንፃ ኮንስትራክሽን በ1ኛ ዲቪዚዮን ጥሩ ተወዳዳሪ ከሆነ በኋላ ቡድኑን ለቀቅኩ፡፡
አዲስ ዘመን:- ቡድኑን ውጤታማ ማድረግ ከቻሉ ለምን ከቡድኑ ጋር አብረው አልቀጠሉም? ወይስ የተሻለ ክለብ ስላገኙ ነው?
አሠልጣኝ አስራት:- ከህንጻ ኮንስትራክሽን ጋር የተለያየሁበት ምክንያት ትንሽ ለየት የሚልና የሚያስገርምም ነው፡፡ በደርግ ዘመን በየመሥሪያ ቤቱ በርካታ የመንግሥት ካድሬዎች ነበሩ፡፡ በአንድ ወቅት ከስፖርት ኮሚሽን የመጡ ሹሞች የእግር ኳስ ክለቦችን እየዞሩ ይጎበኛሉ፡፡ በጊዜው ደግሞ ክለቡ የራሱ ጥሩ ሜዳ እንዲሁም የተጫዋቾች ማደሪያ እና ማረፊያን አሟልቷል። ከመጡት ካድሬዎች መሀል አንዱ ዶክተር «ይህን ቡድን ማሰልጠን እፈልጋለሁ» አለ፡፡ ዶክተሩ ሥልጣን ስለነበረው የህንፃ ኃላፊዎች ጠርተውኝ ሰውዬው ቡድኑን እንዲያሠለጥን እኔም ወደ መደበኛ ሥራዬ እንድመለስ ቀጭን ትዕዛዝ ሰጡኝ፡፡ በወቅቱ ከአሠልጣኝነቱ በተጓዳኝ በግዥ ባለሙያነት እሠራ ስለነበር አሠልጣኝነቱን ትቼ በባለሙያነት እንድሠራ ትዕዛዝ ተላለፈ።
አዲስ ዘመን:- ከህንጻ ከወጡ በኋላ ቀድሞ ተጫዋች የነበሩበትን ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን የማሠልጠን ኃላፊነት እንዴት ሊሰጥዎት ቻለ?
አሠልጣኝ አስራት :- ወደ ጊዮርጊስ ልገባ የቻልኩት በወቅቱ የነበረው አሠልጣኝ ፕሮፌሰር ሲሳይ ዘለቀ መልቀቁን ተከትሎ ነው። በታችኛው ዲቪዚዮን ውስጥ የነበረውን ቅዱስ ጊዮርጊስ እንድረከብ ጥሪ ቀርቦልኝ በደስታ ተቀብዬ ማሠልጠን ጀመርኩኝ። ክለቡን የማሠለጥነው የህንፃን መደበኛ ሥራዬን እየሠራሁ ነበር፡፡ ልምምድ የማሠራው ከመደበኛው ሥራዬ ስወጣ ከ11:00 በኋላ አልያም ደግሞ ወደ ሥራ ከመግባቴ በፊት በሌሊት ነበር፡፡ ይህ ቅዱስ ጊዮርጊስን ወደ ውጤታማነት ከማምጣት አላገደኝም ነበር። በአጭር ጊዜ ውስጥም ክለቡን ወደ 1ኛ ዲቪዚዮን አሳደኩት፡፡
ህንጻ ኮንስትራክሽን እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ተገናኝተው የእኔ ክለብ መሥሪያ ቤቴን በማሸነፉ በህንፃ የነበረኝ ሥራ ተቋረጠ፡፡ ከሥራ መሰናበቴን ተከትሎ ጊዮርጊሶች 300 ብር ይከፍሉኝ ጀመር፡፡ ገንዘቡ ሙሉ ቤተሰብ ለማስተዳደር በቂ የነበረ ባይሆንም ከባዶ ይሻል ነበር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስን እያሠለጠንኩ ክለቡን ለተለያዩ ድሎች አበቃሁት፡፡ የአዲስ አበባ ሻምፒዮና፣ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና እና የጥሎ ማለፍ ዋንጫዎች ባለቤት ሆንን፡፡ ለአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮና ውድድርም ማሳለፍ ችያለሁ፡፡
አዲስ ዘመን:- ከቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ህንጻ ኮንስትራክሽን በመመለስ ማሠልጠን የጀመሩበት አጋጣሚ እንዴት ተፈጠረ? ከዛስ በኋላ የነበረው ሂደት ምን ይመስል ነበር?
አሠልጣኝ አስራት :- በዚያኑ ሰሞን የቀድሞ ክለቤ ህንፃን ዳግም እንዳሠለጥን ቤቴ ድረስ በመምጣት ጥያቄ አቀረቡልኝ ፡፡ ደመወዝ ጭማሪ ተደርጎ ያልተከፈለኝ ደመወዝ ተከፍሎኝ እንድሠራ ተጠየቅሁ፡፡ ነገሩን ከተለያዩ አቅጣጫዎች በማመዛዘን ወደ ህንፃ አሠልጣኝነት ተመለስኩ፡፡ ቃላቸውን ጠብቀውም 420 ብር ወርሀዊ ደመወዜን ሥራ ላይ ባልነበርኩባቸው ወራት አባዝተው ከፈሉኝ፡፡ ብዙ ገንዘብ የቆጠርኩትም ያን ጊዜ ይመስለኛል፡፡ የወር ክፍያዬ ወደ 750 ብር አደገልኝ፡፡ በዚህ ጊዜ ህንፃ ወደ ታችኛው ዲቪዚዮን ወርዶ ነበር፡፡ እኔም ጠንክሬ አሠርቼ ወደ 1ኛ ዲቪዚዮን መለስኩት፡፡ ከዛም ወደ ሜታ ቢራ አመራሁ፡፡ በ100 ብር የደመወዝ ልዩነት፡፡ ከሜታ ቢራ በመቀጠል እርሻ ሰብል፣ ፊናንስ ፖሊስ፣ በድጋሚ ቅዱስ ጊዮርጊስን (ለ9 ዓመታት)፣ አየርመንገድ፣ መከላከያ፣ መብራት ኃይል፣ ባንክ፣ መድን እና ደደቢት የአሠልጣኝነት ህይወቴን ያሳለፍኩባቸው ክለቦች ናቸው፡፡ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ደግሞ የተስፋውን፣ የወጣቱንና ዋናውን ቡድኖች አሠልጥኛለሁ፡፡
አዲስ ዘመን:-በእነዚህ ክለቦች በነበረዎት ቆይታ ያስመዘገቡት ውጤት ምን ይመስል ነበር?
አሠልጣኝ አስራት:- በእነዚህ ክለቦች በነበረኝ ቆይታ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችያለሁ። በተለይ ለሰባት የውድድር ዘመናት በቅዱስ ጊዮርጊስ አሠልጣኝነት ሳገለግል ስድስት የፕሪሚየር ሊግ የሻምፒዮናነት ክብሮችን አግኝቻለው፡፡ ይሄም ለእኔ ትልቁ ስኬቴ ነው። ከመከላከያ ክለብ ጋር የጥሎ ማለፍ ዋንጫን፤ ከመብራት ኃይል ክለብ ጋር የሲቲ ካፕ ዋንጫን እንዲሁም መድንን የብሄራዊ ሊግ ሻምፒዮን አድርጌአለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሰባት ጊዜ በላይ የኮከብ አሠልጣኝነት ሽልማቶችን ማግኘት ችያለው፡፡ ከዚህ አንጻር ስንመለከተው በአሠልጣኝነት ዘመኔ ስኬታማ እና ዕድለኛም ነበርኩኝ ማለት ያስደፍረኛል፡፡
አዲስ ዘመን:-በተጫዋችነት ጊዜ የተነፈጉትን ዕድል በአሠልጣኝነት ዘመን ለመወጣት ችለዋል፡፡ በክለብ ደረጃ ማስመዝገብ የቻሉትን ስኬት በብሄራዊ ቡድን መድገምዎት ይነገራል፡፡ በብሄራዊ ቡድኑ የነበረዎት ቆይታ ምን ይመስል ነበር?
አሠልጣኝ አስራት:- ብሄራዊ ቡድኑን በያዝኩበት ወቅት ውጤታማ መሆን ችያለሁ ማለት እችላለሁ። በክለብ ደረጃ የነበረኝን ውጤታማነት በብሄራዊ ቡድን አሠልጣኝነት በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ ዋንጫ ማምጣት ችያለሁ። ተገቢውን ሂደት ጠብቄ መምጣቴ ለዚህ ረድቶኛል። የብሔራዊ ቡድኑ ኃላፊነት የተሰጠኝ በሂደት ነው፡፡ መጀመሪያ የተስፋ ቡድን አሠልጣኝ ነበርኩ፡፡ በተስፋ ቡድን ያደረግኩት አስተዋፅኦ፣ በክለቦች ዋና አሠልጣኝነት በአገር ውስጥ በዓለም አቀፍ ውድድሮች የነበረኝን ልምድ በመንተራስ የተረከብኩት ኃላፊነት ነው፡፡
መጀመሪያ የያዝኩት የተስፋ ቡድን ከ22 ዓመታት በፊት በተዘጋጀ ውድድር ላይ የተሳተፈ ነው፡፡ ዋናው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመንግስቱ ወርቁ የሚሠለጥን ነበር፡፡ በወቅቱ የተስፋ ቡድኑ የተሳተፈበት ውድድር የናይጀሪያዎቹ ትላልቅ ተጫዋቾች እነ አሞካቺ፤ ያኪኒ ሁሉ የነበሩበትና እነሱዳንም ተጋባዦች ሆነው የተሳተፉበት ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ የተሳተፈችው በወጣት ቡድኑ እና በዋና ብሔራዊ ቡድኑ ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ ሂደት ነው የተስፋ ቡድኑን የገነባሁት፡፡ ከፍተኛ ልምድ ያገኘሁበት ነበር፡፡ በወቅቱ ዋናው ቡድን አንደኛ ደረጃ ሲያገኝ የእኔ ተስፋ ቡድን ሁለተኛ ነበር።
በዚህ መልክ በመጓዝ ዋናውን ቡድን እስከ መረከብ ደረስኩ። እኤአ በ2000 ሩዋንዳ በተዘጋጀው የሴካፋ ውድድር የሰባት ቀን ዝግጅት በማድረግ በመሳተፍ 3ኛ ደረጃ በመያዝ የነሐስ ሜዳሊያ ይዤ መጥቻለሁ፡፡ እ.ኤ.አ በ2001 የነሐስ ሜዳሊያ ካገኘው ስብስብ የተወሰኑ ተጨዋቾችን ይዤ ተሳተፍኩኝ፡፡ ወደ ሩዋንዳ ተጉዘን ውጤት ይዘን መጣን፡፡ ረዳት አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው፤ የቡድን መሪው ደግሞ ዶክተር ኃይሌ ነበሩ /ነብሳቸውን ይማረው/። ከአገሬ ውጭ ዋንጫ ይዞ የመምጣት ህልሙ በ2001 ተሳካልኝ፡፡ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ስንደርስ ህዝቡ ደማቅ አቀባበል አደረገልን። የነበረውን ስሜትም አሁን ድረስ የማይረሳኝ እና ትልቅ ቦታ የምሰጠው ነው። በኢትዮጵያ አዘጋጅነት የተካሄደ አለሙዲን ሲንየር ቻሌንጅ ካፕ የሚል ስያሜ የተሰጠውን የሴካፋን ውድድር ዋንጫን ብሄራዊ ቡድኑ ዳግመኛ በማንሳት ሌላ ታሪክ መሥራት ችለናል።
አዲስ ዘመን: - በእግር ኳሱ ዓለም ከ50 ዓመት ላላነሰ ጊዜ ቆይተዋል፡፡ ከትናንት እስከ ዛሬ ያለውን የአገሪቱን የእግር ኳስ ጉዞ እንዴት ያዩታል?
አሠልጣኝ አስራት:- ጠንካራ ክለብ በሌለበት ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን መፍጠር እንደማይቻል ለመግለጽ ሞክሬያለሁ። ብሄራዊ ቡድኑ እኔ በያዝኩበት ደረጃ ከዓለም 85 ደረጃ ላይ ደርሷል። ያኔ ሴካፋን ያነሳንበት ወቅት ነበር። በወቅቱም ብሄራዊ ቡድኑም በሴካፋ ውድድር ላይ መሳተፍ የለበትም፤ አቅሙ ከዚህ ውድድር በላይ ነው የሚል ሃሳብ መነሳቱን አስታውሳለሁ። አሁን ብሄራዊ ቡድኑ በሴካፋ ውድድር እራሱ እየተንገራገጨ ከምድቡ ማለፍ ሳይችል ቀርቷል። በወቅቱ ትላልቅ አሠልጣኞች ነበሩ። ጥሩ ክለብ የመሥራት አቅምና ብቃት ያላቸው አሠልጣኞች መኖራቸው ብሄራዊ ቡድኑ ውጤታማ እንዲሆን መሰረት ጥሏል። አሁን ላይ የአሠልጣኝነት ሙያው ራሱ ረክሷል።
የሚመለከታቸው የአሰራር ችግሮች አሉ። እነዚህን ዝም ብሎ ከመመልከት ውስጥ ሆኖ ማረቅ ይሻላል የሚል እሳቤ አለኝ። ክለቦች አሠልጣኞችን የሚቀጥሩት ባለሙያው ባለው የሥራ ውጤት አይደለም። ሙያው ወድቋል፤ ረክሷል። በሙያው ውጤታማ የሆኑ አሠልጣኞችን ከመፈለግ ይልቅ አቅሙና ብቃቱ የሌላቸውን መቅጠሩ ላይ ያዘነበለ ተግባር ነው ክለቦች ላይ የሚታየው። የማይሠራው ነው ጥሩ ቦታ የሚሰጠው፡፡ ሃቁን ለመናገር አሁን ኋላፊነት የሚሰጣቸው አሠልጣኞች ምን ውጤት አምጥተው ነው በብሔራዊ ቡድኑ ላይ የተሾሙት? ሂደትን ጠብቀው ነው ወደ ዋናው ብሄራዊ ቡድን መምጣት የሚገባቸው የሚል እሳቤ አለኝ።
አዲስ ዘመን:- ይሄ ለፕሪሚየር ሊጉ ውድቀት ምክንያት ሆኗል ይላሉ?
አሠልጣኝ አስራት :- በሚገባ። ጠንካራ ቡድን አልያም ክለብ ለመገንባት ብቃት ያለው አሠልጣኝ ያስፈልጋል። መሥራት የሚችል አሠልጣኝ መኖር የግድ ነው። ክለቦች የሚፈጽሙት የአሠልጣኞች ቅጥር በተዘረጋ የትውውቅ ገመድ መሆኑ እና፤ ስለ ውጤት ብዙም የማይጨነቁ መሆኑ ጥሩ አሠልጣኝን ፕሪሚየር ሊጉ ላይ ለማየት አልተቻለም። ይሄም በውድድሩ ላይ የራሱን የሆነ መጥፎ ጠባሳን ይዞ መጣ።
አዲስ ዘመን:-የእዚህ ነጸብራቅ ከብሄራዊ ቡድኑ ውጤት ቀውስ ጋር ይዛመድ ይሆን?
አሠልጣኝ አስራት:-በትክክል እንጂ።ብሄራዊ ቡድን የክለቦች ውጤት ነው። ክለብ ላይ ያለውን ተጫዋች ነው ለብሄራዊ ቡድን የምትመርጠው። ደካማ ክለብ ባለበት ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን መጠበቅ የማይታሰብ ነው። በመሆኑም እግር ኳሱ ሙያውን በሚያውቁት አካላት እንዲመራ ማድረግ ይገባል። ይሄን ማድረግ ሲቻል ስፖርቱ ላይ የሚታዩትን ቴክኒካል ችግሮች በመቅረፍ ውጤታማ መሆን ይቻላል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን:- የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ 80ኛ ዓመት ሲከበር፤ የህይወት ታሪክዎትን የሚዳስስ መጽሃፍ እየጻፉ እንደነበር ተናግረዋል። ምን ላይ ደረሰ ?
አሠልጣኝ አስራት :- ጥሩ እየተጓዘ ነው። በዚህ ዓመት ይወጣል ማለት ባልችልም ፤ ለመጽሃፍ የሚሆኑ መረጃዎችን አሰባስቤ ጨርሻለሁ። መረጃውን ወደ ጽሁፍ የመቀየርና መጽሃፍን ለማሳተም የሚያግዝ ስፖንሰር በማፈላለግ ላይ እገኛለሁ። ለተለያዩ ክለቦች ንድፈ ሃሳብ በማቅረብ እንዲያግዙኝ ጠይቄአለሁ። የሌሎች ድርጅቶችን ምላሽም በመጠባበቅ ላይ ነኝ፡፡
አዲስ ዘመን: - ከስታዲየም ውጪ ያለው የግል ህይወትዎ ምን ይመስላል?
አሠልጣኝ አስራት:-ጥሩ ባል፣ ጥሩ አባት እንዲሁም ጥሩ አያት ነኝ። ከባለቤቴ ጋር 40 የትዳር ዓመታትን አሳልፈናል።በቆይታችንም አምስት ልጆችን አፍርተናል፡፡ ከእነርሱ ደግሞ ሰባት የልጅ ልጆችን በማፍራት አያት ለመሆን በቅተነናል።
አዲስ ዘመን: -ስለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አሠልጣኝ አስራት:- እኔም ልምዴን እንዳካፍል አክብራችሁ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ።

Published in ስፖርት
Wednesday, 07 February 2018 17:09

የሳምንቱ ፎቶ

«አ
ት ያድርሰን!»


ከሀምሳአመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ በቅርቡም በአዲስ አበባ ከተማ ሰላሳኛውን ጉባኤ ሲያካሂድ መቆየቱ ይታወሳል። የዘንድሮውን ጨምሮ በየጊዜው በሚደረጉ ስብሰባዎችም ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የሚመጡ መሪዎችና ሚኒስትሮች ተሳታፊ የመሆናቸው አጋጣሚ ተቋርጦ አያውቅም። እንግዶቹ እንደመገናኘታቸው ሁሉ ሲለያዩግድ ነውና «ለከርሞ ያብቃን፣ ከአመት አመትም ያድርሰን! በሚል አይነት ተቃቅፈው በእንዲህ መልኩ ይሰነባበታሉ።

 

Published in መዝናኛ
Wednesday, 07 February 2018 17:07

በሰላም ተመልሰናል

 

የጉዞ ማስታወሻ

ወላይታ ሶዶ ከተማ የሄድንበትን ጉዳይ አጠናቀን ወደ ሸገር ለመመለስ በያዝነው ቀጠሮ መሰረት ሁላችንም በሰአቱ ተገናኝተናል። ሌሊቱ እጅግ ከባድ ንፋስ የነበረበት በመሆኑ አብዛኛው ሰው ጭንቀት ውስጥ እንደነበረ ያወራል። ንፋሱን ተከትሎ የከተማዋ መብራት መጥፋቱ ደግሞ በተለይ ለእንደኛ አይነቶቹ እንግዶች የተመቸ አልነበረም።
በጠዋቱ ከአፋችን ጣል ያደረግነው ቁርስ መልካም ነበር። መንገድን በማለዳው መጀመር ጥሩ እንደሚሆን አብዛኛው የተስማማ በመሆኑ በመጠባበቅ የባከነ ጊዜ የለም። ሁሉም መንገዱን እያሰበ ቤቱ ደርሶ ስለሚያደርገው አንዳንድ ጉዳይ ያስባል። ከቤተሰብና ከወዳጅ ጋር ይደዋወላል፤ ቀጠሮ የያዘም አልጠፋም።
ወላይታ ሶዶ ከተማን ከእነ አስፈሪና አስደንጋጭ ሞተር ሳይክሎችዋ ግርግር ተሰናብተን ጸጥ ያለውን መንገድ ስንጀምረው ጸሀይ እምብዛም አልከረረችም። በመጀመሪያው ጉዞና በስራ ቆይታችን ይበልጥ ተቀራርበናልና በመካከላችን የባዕድነት ስሜት አይስተዋልም። ይልቁንም ጨዋታና ቀልዱ ተሟሙቆ ጉዟችን በተለየ ድምቀት የተሞላ ሆኗል።
አሁን ቀድመን በመጣንበት መንገድ እየተመለስን ነው። ቦዲቲን አልፈን የዳሞት ጋሌዋን ቡኔ ከተማን ተሻግረናል። በዚህች ከተማ ጥቂት የማይባሉ የፈረስ ጋሪዎች የመንገዱን ዳር ይዘው ከመኪኖች ጋር እየተጋፉ ያልፋሉ። ጋሪዎቹ ያሳፈሯቸው ሰዎች ቁጥራቸው ከመጠን በላይ ቢሆንም አደጋውን የፈሩት አይመስልም። አንዱ ጋሪ እንዳለፈ ሌላውም በተመሳሳይ መንገደኞችን እንደደራረበ ይከተለዋል።
ከፊትና ከኋላቸው ሽው እያሉ የሚያልፉ ከባድ መኪኖች ስለነሱ መኖር ግድ አልሰጣቸውም። ሁሉም መንገዱን በእኩል መብት እየተጋሩ ይሽቀዳደማሉ። ይህ ለሌላው ተመልካች እንጂ ለእነሱ ምንም ማለት እንዳልሆነ ተረዳሁና በእጅጉ ተገረምኩ። ምን አልባትም ይህ መንገድ ብዙ ጊዜ የከፋ የሚባል አደጋን ያስተናግድ ይሆናል።
የሀድያዋ ሾኔ ከተማን ስንሄድ እንዳየናት ሁሉ አሁንም እያለፍንባት ነው። ሞቅ ደመቅ ብላለች። ይህን አካባቢ ጨምሮ ከመንገዱ አለፍ ያለው ስፍራ በባህርዛፍ አጀብ ተሞልቷል። እሱም ብቻ ሳይሆን ያለፍንባቸው አብዛኞቹ አካባቢዎች ባህርዛፍ ጥላና ከለላቸው፣ ውበትና መናፈሻቸው ስለመሆኑ አስተውለናል። ይሁን እንጂ የአንዳንድ ጊቢዎች አጥር በባርዛፍ ሳይሆን በሳጣራ የተከበረ መሆን እያስገረመኝ ነው።
ዱራሜን ጨምሮ በአጭር ርቀት የተመሰረቱትን ከተሞች እያለፍን ሀላባ ገብተናል። የሀላባ አካባቢ በበርበሬ ምርት እንደመታወቁ ገና ወደ ቁሊቶ ከተማ ስንገባ በርበሬን በየቦታው በማየታችን አልተደነቅንም። በየጆንያው ተሞልቶ በመንገዱ ዳርቻ የተቀመጠው በርበሬ ሰአቱ ገፋ ፣ቀኑም ሞቅ ሲል ለደማቁ የቅዳሜ ገበያ እንደሚቀርብ መገመት ይቻላል።
ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ እንደአማራጭ ከሚጠቅሙ መንገዶች መካከል ወደ ሀዋሳ ዝዋይና አዳማ የሚገነጠለውን የቀኝ መንገድ ትተን በቁሊቶ ከተማ መሀል ለመሀል ሰንጥቆ ወደ ሸገር የሚያደርሰውን የግራ አቅጣጫ ይዘናል። ይህ መንገድ ጉዞን የሚያሳጥር በመሆኑ ብዙዎች ይመርጡታል። እኛም ቀድመን ለመግባት ባለን ፍላጎት የተነሳ የመጀመሪያ ምርጫችን ይህኛው አቅጣጫ ሆኗል።
መንገዱን ጥቂት አለፍ ብለን ወደ ከተማዋ መግባት እንደጀመርን ከኛ ፊት ለፊት ሁለት መኪኖች ከፊትና ኋላ ተጠጋግተው እንደቆሙ ተመለከትን። የመጀመሪያው በተለምዶ «ኦባማ» የሚባለው የጭነት መኪና ነው። ከሱ ተከትሎ የቆመው ደግሞ ቅጥቅጥ አይሱዙ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ። እኛ ከዚህ መኪና ጀርባ ስንደርስ ከመካከላችን ሌላ ተሽከርካሪ አልነበረም።
ሁለቱም መኪኖች ድንገት የመቆማቸው ምክንያት ምን እንደሆን ባይታወቅም አልፎ ለመሄድ ግን ረጅም ደቂቃዎችን ወስደዋል። የእኛ ኮስትር የሚባለው መኪና ደግሞ እነሱ መንገዱን ካለቀቁለት አልፎ ለመሄድ አይቻለውም። የእኛን ጨምሮ በተከታታይ በሰልፍ የቆሙት መኪኖች መንገዱን ዘግተውት እንደቆዩ ድንገት የፊተኛው መኪና እንደመንቀሳቀስ አለና ወደፊት ተፈተለከ። ይህ መሆኑ ለእኛ ለቸኮልነው መንገደኞች እፎይታ ነው። በቶሎ ለመግባት ለተያዘው ቀጠሮ በሰአቱ ለመድረስ።
የተዘጋጋው መንገድ በፊተኛው መኪና ቦታ መልቀቅ መከፈቱ ሲታወቅ ከእሱ ኋላና ከእኛ ፊት የነበረው የህዝብ ማመላለሻ ተከትሎት ለመጓዝ ነቅነቅ አለ። ይህ ሁሉ ሲሆን የኛው ኮስትር ከቆመበት ሳይንቀሳቀስ የእሱን አልፎ መሄድ እየጠበቀ ነበር። ድንገት ወደ ኋላ መምጣት የጀመረው መኪና ሁላችንንም አስደንግጦናል። ሾፌራችን የእሱን አለአግባብ ወደ ኋላ መምጣት እንዳየ ደማቅ ጡሩምባውን አስተጋባ። ጲጲጲጲ...ጲጲጲ..
መኪናው ወደ ኋላ መምጣቱን ቀጥሏል። የእኛ ጨኸትና የኮስትራችን ጡሩምባም እንዲሁ። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የኋላ ማርሽ ያስገባው አሽከርካሪ መስሚያ ጆሮ አልነበረውም። በመጣበት ፍጥነት እየተጠጋ ከደረሰብን በመኪናችን ላይ ጉዳት፤ በእኛም ላይ አደጋ መድረሱ ላይቀር ነው። የእኔ አዕምሮ በዛች ቅጽበት ይህንኑ እያሰበ ነው። ጅምር ሀሳቤን ከዳር ሳላደርሰው ግን የሆነው ሁሉ ሆነ። ተሽከርካሪው ወደ ኋላ መምጣቱን ባለማቆሙ የእኛን መኪና ግንባር በኋለኛው አካሉ ጠረመሰው። ‹‹ጓ..ጓ. ከሸሸሽሽ ... የሚል ድምፅ ጎልቶ ተሰማ፡፡ በአንድ አፍታ የነበረው ሁሉ እንዳልነበረ ሆነ። ሁላችንም ተሸማቀቅን ፣መስታወታችን ደቀቀ። የፈራነው ደርሶም ያልታሰበው አደጋ ተከሰተ።
ይህ ከሆነ በኋላ ሁላችንም በድንጋጤና በንዴት እንደተሞላን ከመኪናችን ፈጥነን ወረድን። ወዲያውም ረጃጅም ባለቀለም ባርኔጣዎችን የደፉ የሀገሬው ሰዎች ዙሪያችንን ከበቡን። የጡሩምባውን ጥሪ ሳይሆን የመኪናችንን መጎዳት ያወቀው አሽከርካሪ ግን እንደኛ የደነገጠ አይመስልም።ደረቱን ነፍቶና እጁን ኪሱ ከቶ ዝነጣ በሚመስል አረማመድ ቀረበን።
ሁሉም ምንነካህ? በሚል ጥያቄ ሊሞግተው ተዘጋጅቷል። እሱ ግን የማንንም ንዴትና ድንጋጤ ከምንም አልቆጠረም። የተመልካቾች ትርምስና የአንዳንዶች ትክክለኛ አስተያየትም አብሽቆታል። «አይን አይቶ ልብ ይፈርዳል» እንዲሉ አብዛኛው ሰው ያየውን ሳይደብቅ በእውነታው ሞገተው፤ መሰከረበትም። ይህን የተረዳው አሽከርካሪ መኪናችንን ከፊትና ኋላ እየቃኘ የሚገርምና እጅግ የሚያበሽቅ ምላሹን ሰጠ።
በመንገድ ትራፊክ ህግና በአደጋ ጊዜ ከኋላ ያለ መኪና ጥፋተኛ ነው የሚባለውን ጫፍ ብቻ ይዟል። ይህ ኢምንት ዕውቀቱ ደግሞ ከፈጸመው ስህተት መንጭቆ እንደሚያወጣው ገምቷልና ሽንጡን ገትሮ ስህተቱን ወደ እኛ አሽከርካሪ ሲያላክክ እፍረትም ድንጋጤም አልተነበበበትም። በማንነቱ ላይ የሚስተዋለው የጥሩ ስነምግባር ጉድለትም ሁላችንንም ከጠብ ባላነሰ ሙግት ውስጥ ከቶናል።
ጉዳዩን ህግ ሊፈታው ግድ ነውና የአካባቢው ትራፊኮች እስኪመጡ ጠበቅን። ምስጋና ለሀላባ ቁሊቶ ከተማ ትራፊክ ፖሊሶች ይሁንና ጊዜ ሳይፈጁ በርከት ብለው ደረሱልንና ምልክትና ፕላን ተደርጎ ክርክሩ ቀጠለ። ጉደኛው ሾፌር ትራፊኮቹን ሲመለከት ይባስ እንደመመናጨቅ ብሎ ሊያዋክባቸው ሞከረ። እነሱ ሁኔታውን አውቀዋልና ፈጥነው የመንጃ ፈቃዱን ጠየቁት።
ሾፌሩ የተጠየቀውን በተግባር ከማሳየት ይልቅ መንጃ ፈቃድ እንደሌለው ተናገረ። ቆይተን እንደሰማነው ደግሞ በዕለቱ በሌላ አካባቢ በፈጸመው የህግ መተላለፍ ተቀጥቶ ነበር። ምን አልባትም የመንጃ ፈቃዱን ያለመያዙ ምክንያት ይህ ሊሆን ይችላል። ሾፌሩ ይህ ድርጊቱ ሳያንስ ለትራፊኮቹም «ገጨሁ» ሳይሆን «ተገጨሁ» ሲል ለማሳመን መሞከሩ አበሳጭቶናል። ዝምተኛው የእኛ ሾፌር ሳይቀር በንዴት በግኖ እየተጨቃጨቀ ነው። እኛን ጨምሮ ሌሎች ተመልካቾችም ያዩትን ሁሉ ሊያስረዱ ሞክረዋል።
ጉዳዩ በመተማመን የሚፈታ አልሆነም። የሀላባ ጸሀይ ልክ እንደበርበሬው አቃጥሎ እየፈጀን ነው። በጭቅጭቅ የባከነው ጊዜ ቀላል አልሆነም። በጊዜ ደርሶ ያሰቡትን መከወንንና ለቀጠሮ መድረስ ይሉት ነገር ውሃ በልቶታል። አሁን ከሁለት ሰአት ተኩል ያላነሰ ጊዜን በመጨቃጨቅ አሳልፈናል። መስማማትና ወደ አንድ ሀሳብ መምጣት የሚታሰብ አልሆነም። ይህ ከሆነ ደግሞ ቀጣዩን በህግ አግባብ መዳኘት ግድ ብሏል።
በዚህ መሀል የእኛው የጉዞ አካል የነበረ የወላይታ ሶዶ አውቶቡስ በድንገት ደረሰ። በውስጡ የነበሩ ተጓዞች እኛን በዚህ መልኩ ማግኘታቸው አስደንግጧቸዋል። ሁሉም አንድ በአንድ እየወረዱ ሁኔታውን እስኪያውቁትም በታላቅ ድንጋጤ ውስጥ ነበሩ። ቆይቶ የትራፊኮቹ ሀሳብ ሁለቱንም ሾፌሮች ወደ ጣቢያ ማድረስ ሆነ። ይህ ከሆነ ደግሞ መኪናው ታስሮ ሾፌራችን ሊንገላታ ነው።
የመጨረሻው ሀሳብ ላይ እንደተደረሰ ሁላችንም ተያይዘን ወደ ጣቢያው አመራን። ተገቢውን ሂደት ለመፈጸም ሾፌሩ እዛው መቆየት ይኖርበታል። ኢንሹራንስ፣ ፕላን እና ሌሎችም ጉዳዮች የራሳቸው ጊዜና ቦታ ያስፈልጋቸዋል። ደግነቱ እኛን ሲጠብቅ የነበረው የዩኒቨርሲቲ አውቶቡስ ሁላችንንም ይዞ ለመሄድ ተዘጋጅቷል።
አብሮን የወጣውን ሾፌር ከመንገድ ትተነው ልንሄድ ግድ ሆኗል። ከዚህ ውጭ ምርጫ አልነበረንም። እሱን የኋልዮሽ እያየን ወደተዘጋጀው መኪና ስንገባ የሁላችንም ልብ በግማሽ ቀርቶ ነበር። ቀሪው መንገድ መልካም ሆነልን። ይበልጥ ደግሞ የእኛ ሾፌር ጉዳዩን ጨርሶ እየተከተለን መሆኑን ስንሰማ እጅጉን ተደሰተን። አሁን ሁላችንም ባሰብነው ጊዜ ሳይሆን ፈጣሪ ባለው ሰአት በሠላም ተመልሰን ወደ የቤታችን ገብተናል። እፎይ! ተመስገን!

መልካምሥራ አፈወርቅ

Published in መዝናኛ

የግድቡ ግንባታ ዕውን መሆን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ውስጧ እጅግ ተረብሿል፡፡ እናም የግድቡ ግንባታ እንዲቆም ያላትን አቅም ሁሉ ከመጠቀም ወደ ኋላ አላለችም፡፡ ብዙ ሞክራለች፣ ጥራለች፣ ተጉዛለች-ግብፅ፡፡
ዛሬም ቢሆን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙርያ ግብፅ ይህ ነው የሚባል የጠራ አቋም የያዘች አይመስልም፡፡ በየጊዜው የአቋም መለዋወጥ ይታይባታል፡፡ ግድቡ በሚያደርሰው ተፅዕኖ ዙርያ የቴክኒክ ቡድን ተዋቅሮ ጥናት እንዲያካሂድ ስምምነት ላይ ቢደረስም ብዙም አልተዋጠላትም፡ የቡድኑ ውጤት ገና ይፋ ሳይሆን ግብፅና ኢትዮጵያ ለብቻችን እንደራደር እስከ ማለት ሞክራለች፡፡ ለዛውም ራሷ የመረጠችውን አደራዳሪ አካል ይዛ በመቅረብ፡፡ ይህን መሰሉ አካሄድ ተገቢነት የለውም ስትባል ደግሞ ወደ መለሳለሱ ትመጣለች፡፡
ከአሁኑ የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በፊት የነበሩት መሪዎች ግድቡን ለማስቆም ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፡፡ የኃይል እርምጃ እስከ መውሰድ እንደሚገደዱ ለማስፈራራት ሞክረዋል፡፡ ‹‹አንዲት የውሃ ጠብታ እንድትነካብን አንፈልግም››በማለት የእአአ 1929 እና 1959 የቅኝ አገዛዝ ውሎችን አጣቅሰዋል፡፡
የፕሬዚዳንት አልሲሲ ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ነገሮች መሻሻል እያሳዩ ነው፡፡ የአባይን ውሃ በፍትሃዊነት የመጠቀሙን ሂደት በውይይት መስመር ለማስያዝ ፕሬዚዳንቱ የተሻለ ፍላጎት እያሳዩ እንደሆነ ነው የሚገለፀው፡፡ ይህም ሆኖ ታዲያ በተቻለ መጠን የግድቡ ግንባታ ቢገታ ደስታ እንጂ ቅሬታ አይፈጥርባቸውም ይላሉ የዘርፉ ምሁራን፡፡ ለዚህ ደግሞ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ከሁለት ዓመት በፊት አትዮጵያን ሲጎበኙ አባይን በጋራ ስለ መጠቀም የገቡትን ቃል ‹‹ግብፅ ታሪካዊ የውሃ ድርሻዋን አታስነካም ›› ዓይነት ይዘት ያለው መልዕክት በማስተላለፍ ወደ ኋላ ለማፈግፈግ መሞከራቸውን በአስረጅነት ያቀርባሉ፡፡
በቅርቡ የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ 30ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ሲካሄድ የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን መሪዎች የሚወያዩበትን መልካም አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል፡፡ መሪዎቹ በህዳሴ ግድብ ዙርያ የመከሩ ሲሆን በዚህም በተናጠል ሳይሆን እንደ አንድ አገር መጓዝ እንዳለባቸው ስምምነት ላይ መድረሳቸው ነው የተሰማው፡፡
መሪዎቹ በህዳሴ ግድብ ዙርያ ብቻ ሳይገደቡ በሌሎች የጋራ ጉዳዮች ዙርያ ለመሥራት ከስምምነት ላይ እንደ ደረሱ ተገልጿል፡፡ በመሪዎች ደረጃ በዓመት አንድ ጊዜ እየተገናኙ በጋራ ጉዳዮች ለመወያየት፣ ለመነጋገርና አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ተስማምተዋል፡፡
የሦስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይና የውሃ ሀብት ሚኒስትሮች በህዳሴ ግድቡ ግንባታ ላይ ለሚደረጉ ቀጣይ ውይይቶች ከአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ለመሪዎች ሪፖርት እንዲያቀርቡ መመርያ እንደተላለፈ ነው የተሰማው፡፡ የአገራቱን የሕዝብ ለሕዝብና የኢኮኖሚ ትስስር ማጠናከር እንደሚገባም ውይይት ተደርጎ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፤ ለዚህም የሦስትዮሽ የመሠረተ ልማት ፈንድ እንዲቋቋም ተወስኗል፡፡
ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በህዳሴ ግድቡ የተነሳ ወደ ግጭት እንደማይገቡ ፕሬዚዳንት አልሲሲ መናገራቸውን የግብፁ አህራም ድረ ገፅ ዘግቧል፡፡ በሶስቱ አገራት መካከል ግጭት እንደሌለ ማረጋገጣቸውም ነው የተመለከተው፡፡ ‹‹የግብፅ ፍላጎት ከኢትዮጵያና ሱዳን ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ሶስታችንም አንድ ቃል ነው የምንናገረው›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ ችግሮችን በውይይት በመፍታት ለመፍትሔ እንደሚጥሩ ጠቁመዋል፡፡
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚህ ሻኩሪ በበኩላቸው ከህዳሴ ግድቡ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቴክኒካል ጉዳዮችን በአንድ ወር ውስጥ ለመፍታት ከስምምነት መደረሱን ገልፀዋል፡፡‹‹ በህዳሴ ግድብ ዙርያ አደራዳሪ አካል አይኖርም›› ሲሉም ተደምጧል፡፡ ይህ ደግሞ ‹‹ግብፅ ዓለም ባንክ ያደራድረን›› በሚል ያቀረበችው ምክረ ሃሳብ ትክክል አለመሆኑን ለመቀበሏ ማሳያ እንደሆነ የሚጠቁሙ አሉ፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ‹‹አደራዳሪ አያስፈልግም›› በማለት የመመለሷን ተገቢነት ደረጃ ከፍ ያደርገዋል፡፡
የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር በሶስቱ አገራት መካከል ምንም ዓይነት ግጭት እንደሌለ መናገራቸውን ዘገባው ያመለክታል፡፡
በህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙርያ የግብፅ መገናኛ ብዙኃን የተዛቡ መረጃዎችን በመልቀቅ ውዥንብር ሲፈጥሩ ይስተዋላል፡፡ የህዳሴው ግድብ የግብፃውያንን የመኖር ህልውና እስከ መፈታተን የሚደርስ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር በተደጋጋሚ ሲዘግቡ ይደመጣል፡፡ ስለሆነም ህዝቡ ግንባታውን እንዲቃወም ለማነሳሳት ይሞክራሉ፡፡ በዚህ ዙርያም ኢትዮጵያ የግብፅ መንግስት ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስባለች፡፡ የሶስትዮሽ ውይይቱ በዚህ በኩልም ጥሩ ውጤት ያመጣ ይመስላል፡፡ ፕሬዚዳንት አልሲሲ ከህብረቱ ስብሰባ መልስ የአገራቸውን መገናኛ ብዙኃን አስጠንቅቀዋል፡፡
‹‹በህዝቡ ላይ ስጋትን የሚያጭሩና ሌሎች አካላትን የሚያስጨንቁ መረጃዎችን ማቅረብ የለባችሁም፡፡ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል መፍትሔ አለን፡፡ ጉዳዩን የሚከታተል ኮሚቴም ተቋቁሟል›› ብለዋል፡፡
የሶስቱ አገራት መሪዎች ለአገራቸውና ለህዝባቸው በሚጠቅሙ የጋራ ጉዳዮች ዙርያ በትብብር ለመስራት ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር መስማማታቸውን የሚናገሩት ደግሞ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢብራሂም ጋንዱር ናቸው፡፡ አገራቱ አንድነታቸውን በማጠናከር በአገራቱ የሚከናወኑ ልማቶችን ለማፋጠንና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለማጎልበት ከስምምነት መድረሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለሱዳን ትሪቡን አስታውቀዋል፡፡ በአገራቱ የሚከናወኑ ፕሮጀክቶችን በገንዘብ ለመደገፍ የሚረዳ ፈንድ ለማቋቋም ከስምምነት መደረሱም ሂደቱን ለማጠናከር ይረዳል፡፡
ከህዳሴው ግድብ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዮች ለመከታተል የየአገራቱን የውጭ ጉዳይና የውሃ ሚኒስትሮችን በማካተት የተቋቋመው ኮሚቴ በአንድ ወር ውስጥ ለመሪዎቹ ሪፖርት ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ግድቡ የኢትዮጵያ ቢሆንም ሶስቱንም አገራት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
መሪዎቹ በዚህ ደረጃ ላይ መስማማታቸው የሚደገፍና የሚበረታታ ሂደት ነው፡፡ በተለይም ግብፅ ነገሮችን በውይይት ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም ማሳየቷ ይበል ያሰኛል፡፡ ስምምነቱን ወደ መሬት በማውረድ በኩልም የሚጠበቅባትን መወጣት ይኖርበታል፡፡
አንድ ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ የውሃ ምህንድስና ምሁር የግብፅ ስምምነት ለሌላ አማራጭ ፍለጋ ለዕድሜ ማራዘሚያነት እንዳይውል ስጋት አላቸው፡፡ ግብፅ በተለያዩ ጊዜያት የአቋም ለውጥ ማድረጓን ለስጋታቸው በምክንያት ይጠቅሳሉ፡፡ ከፊቷ የተደቀነው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በተፋሰሱ አገራት ጥሩ ተቀባይነትን እንዲያገኝ ከማለም ጋር ሊያያዝ እንደሚችልም ነው የጠቆሙት፡፡
ይህም ሆኖ ግን በመሪዎቹ መካከል የተደረገው ውይይት የተሻለ መግባባትን ለመፍጠርና ለቀጣዩ ጉዞ ጥርጊያውን ለማሳመር እንደሚያግዝ ተመልክቷል፡፡ የሶስትዮሽ ውይይቱ በኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን አገራት መካከል በህዳሴው ግድብ ላይ ይፈጠሩ የነበሩ ጥርጣሬዎችን ለማጥራትና አንድ የጋራ አቋም እንዲይዙ ማስቻሉን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አስታውቋል፡፡
የሶስቱ አገራት መሪዎች ባደረጉት ምክክር በግድቡ ዙሪያ እንደ አንድ አገር ማሰብ እንዳለባቸው አቋም ከመያዛቸውም በላይ በመሰረተ ልማት ለመተሳሰር የሚያስችል ዕቅድ ነድፈዋል፡፡ ሶስቱን አገራት በመንገድ፣ በባቡርና በሃይል መስመር ለማገናኘት የሚነደፉ ፕሮጀክቶችን ዕውን ለማድረግ ፈንድ እንዲቋቋም መግባባት ላይ የተደረሰውም መወያየትና መግባባት በመቻሉ ነው፡፡
ግብፅ አሁን ላይ ያሳየችውን አቋም አጠናክራ ከቀጠለች ችግሮች በውይይት መፈታታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ባለሥልጣናቱ እውነታውን ለህዝቡ በማስረዳት ህዝቡ በህዳሴው ግድብ ግንባታ ዙርያ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የጋራ ጉዞ መግባባቱ ለአንድ ሰሞን ሳይሆን ለዘላቂ መፍትሄ ሊሆን ግድ ይለዋል፡፡ ያኔ የጋራ ጉዞው የጋራ ሀብቱን በፍትሃዊነት የመጠቀም ዕውነታውን ያረጋግጣል፡፡

 በጋዜጣው ሪፖርተር 

Published in ፖለቲካ

በቢዝነስ አስተዳደር ሶስተኛ (ፒ ኤች ዲ) ዲግሪ ይዘዋል፡፡ ለ17 ዓመታት በተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ዩኒቨርስቲዎች አስተምረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ በመሆን አገራቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ-ዶክተር አንዱዓለም አድማሴ፡፡
ሁሉንም የአገሪቱን የቆዳ ሽፋን በሞባይል አገልግሎት ማዳረስ ተችሏል? የኢተርኔትና የሞባይል አገልግሎት ሆን ተብሎ እንዲቋረጥ ይደረጋል ይባላል? ተቋሙ በአህጉርና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተሸላሚ መሆኑ ከሚሰጠው አገልግሎት ጋር ሲነፃጻር እንዴት ይገለፃል? በዘርፉ ፈተናዎችና በመሰል ጉዳዮች ዙሪያ ከዶክተር አንዷለም ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እነሆ፡፡
አዲስ ዘመን፡ -ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቱን የተቀላጠፈና ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ምን ምን ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ?
ዶክተር አንዱዓለም፡- ኢትዮ ቴሌኮም ከተመሰረተ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ተቋም ነው፡፡ የዕድሜውን ያህል ኢንቨስት ተደርጎበታል ማለት ግን አይቻልም፡፡ ኢንቨስትመንቶቹ የዛሬ 10 ዓመት ነው ዘግይተው የተጀመሩት፡፡ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ተደርጎ የሞባይል አገልግሎት የማስፋፊያ ስራ ተካሄደ፡፡ይህም የሞባይል አገልግሎት ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረበት ነው፡፡
ባለፉት ዓመታት መንግስት ለትምህርት፣ ለግብርናና ለጤና ትኩረት ሰጥቶ ኢንቨስት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ወደ ኢንዱስትሪውና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ነው መሄድ ያለብን በሚል አቅጣጫ አስቀመጠ፡፡ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂውን ለማዘመን ደግሞ ወደ ኋላ ሲንቀራፈፍ የነበረውን ቴሌኮም የማዘመን ስራ መቅደም አለበት፡፡በዚህ ጊዜ የነበረው የኔት ወርክ ቴክኖሎጂ አቅም ከአገሪቱ ዕድገት ጋር መራመድ ተሳነው፡፡ ብዙ ፋብሪካዎች፣ ዩኒቨርስቲዎችና ሌሎች ተቋማት የሚፈልጉትን የቴሌኮም አገልግሎት ማቅረብ አልቻለም፡፡ እናም ተቋሙ ፈርሶ አዲስ ተቋም ይቋቋም ወይንስ ያለውን እየጠገንን እንሂድ የሚሉ አስተሳሰቦች ተነሱ፡፡
በሀሳቦች ፍጭት አፍርሶ መገንባት የሚለው የበላይነት በማግኘቱ እኤአ በ2010 ፍራንስ ቴሌኮም በ30 ሚሊዮን ዩሮ ማኔጅመንቱን ማስተዳደር ጀመረ፡፡ ኩባንያው የተቋሙን የውስጥ አደረጃጀት በመቀየር ከወረቀት ነጻ የሆነ የአሰራር ስርዓት በመፍጠር ሊያዘምነው ችሏል፡፡
ከመሰረተ ልማት አኳያም ከአስር ዓመት በፊት የተገነባው የቴሌኮም መሰረተ ልማት የኔት ወርክ አቅም እያደገ የመጣውን የተጠቃሚውን ቁጥር ሊሸከም አልቻለም፡፡ የሚሸከመውም ከ20 ሚሊዮን ያልበለጠ ደንበኛ ነበር፡፡ይህንን አቅም ለማጎልበት ከሶስት ዓመት በፊት በአንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር የቴሌ ኮም መሰረተ ልማት የማስፋፊያ ፕሮጀክት ተግባራዊ ተደረገ፡፡
አገሪቱን በ13 የቴሌኮም ሰርክሎች በመክፈል ለሶስት የተለያዩ ኩባንያዎች ተሰጥቶ የማስፋፊያው ስራ መካሄድ ጀመረ፡፡ በዚህም ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ማለትም የሁለተኛው ትውልድ(2ጂ)፣የሶስተኛው ትውልድ(3ጂ)፣አራተኛው ትውልድ(4ጂ) የቴሌ ኮም አገልግሎት የሚሰጡ ማስፋፊያዎች ተደርገዋል፡፡ ለምሳሌ 4ጂ ላይ ጥቂት የአፍሪካ አገሮች ናቸው ኢንቨስት ያደረጉት፡፡ ከኢንፎርሜሽን ስርዓትም ዘመናዊ የተባለው ነው የተዘረጋው፡፡ እናም እያየንና እያጠናን ደንበኞች የሚፈልጉትን ምርቶችና አገልግሎቶች እያቀረብን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ጊዜ ሁሉንም የአገሪቱን የቆዳ ሽፋን በሞባይል አገልግሎት ማዳረስ ተችሏል?
ዶክተር አንዱዓለም፡- አንዳንድ ክፍተቶች ቢኖሩም በአሁኑ ጊዜ 85 በመቶ የአገሪቱን የቆዳ ሽፋን በኔት ወርክ መሸፈን ተችሏል፡፡ ሆኖም የኔት ወርክ ችግር በሚታይባቸው ቦታዎች የዛሬ ስድስት ዓመት ዲዛይኑ ሲሰራ ህብረተሰብ ያልሰፈረባቸው ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ አካባቢ የህዝብ ቁጥር በመጨመሩ ኔት ወርኩ ተጨናንቆ የሚፈለገውን አገልግሎት በጥራት የማይሰጥበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡
ከመልክዓ ምድራቸው አቀማመጥ የተነሳ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የተቸገርንባቸው ቦታዎችም አሉ፡፡፡ለምሳሌ ሰሜን ጎንደር ዞን ሄሊኮብተር ተጠቅመን ነው ታወሮችን ተራራ ላይ ማውጣት የቻልነው፡፡ እንደዚህ አይነት ችግር ካጋጠመ እንጂ በአጠቃላይ 85 በመቶ የአገሪቱ የቆዳ ሽፋን በ2ጂ ፣3ጂና 4ጂ ኔት ወርክ የተሸፈነ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሰሜን ጎንደር ዞን በየዳና ጠለምት ወረዳዎች የሞባይል አገልግሎት በከፊል እንደሚያገኙ ነዋሪዎች ቅሬታ አቅርበው ተቋማችሁ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ችግሩን እንደሚፈታ ቃል ገብቶ ነበር፡፡አሁን ችግሩ ተፈትቷል?
ዶክተር አንዱዓለም፡- ገና አልተፈታም፡፡ የውጭ ምንዛሬ የማግኘቱ ሂደት በመራዘሙ ዕቃዎቹን በፍጥነት ከውጭ ገዝቶ ማስገባት አልተቻለም፡፡ አሁንም ጥረት እያደረግን ነው፡፡ በልዩ ሁኔታ ለብቻው ነጥለን መፍትሔ ለመስጠት እየሞከርን ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም ትልቁ ማነቆ የሆነብን የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ነው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች አሁንም ክፍተቱ አለ፡፡
አዲስ ዘመን፡-በአሁኑ ጊዜ ኢትዮ ቴሌኮም ምን ያህል ደንበኞች አሉት?
ዶክተር አንዱዓለም፡- ከ62 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የሞባይል፣ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ደግሞ የመስመር ስልክ ደንበኞች አሉን፡፡ በአጠቃላይ ደንበኞቻችን ከ63 ሚሊዮን በላይ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡-የኢንተርኔት አገልግሎት ለህብረተሰቡ ምን ያህል ተደራሽ ነው?
ዶክተር አንዱዓለም፡-ውቅያኖስን አቋርጦ በጅቡቲ ፣በሱዳንና በኬንያ መግቢያ በሮች በኩል የሚመጣና ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ መሬት ውስጥ የተቀበረ (መስመር) ኬብል አለ፡፡ ስለዚህ መንገድና ህንጻ ሲገነባ መሬት ውስጥ የተቀበሩት ኬብሎች ከተቆረጡ አገልግሎቱም አብሮ ይቋረጣል፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ የተቀበሩት ኬብሎች እርስ በርሳቸው እንዲጠላለፉ(እንዲገናኙ) ተደርጓል፡፡ አንዱ ቢቆረጥ በሌላው መስመር አገልግሎት መስጠት ይቻላል፤ለመጠገንም ጊዜ ይሰጣል፡፡ ወደ ክልሎች የተዘረጋው ግን አንድ መስመር በመሆኑ እሱ ከተቆረጠ አገልግሎቱም ይቋረጣል፡፡እነዚህ ችግሮች በአገልግሎታችን ላይ እክል ይፈጥራሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኢተርኔትም ሆነ የሞባይል አገልግሎት ሆን ተብሎ እንዲቋረጥ ይደረጋል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ይህ ምን ያህል እውነትነት አለው?
ዶክተር አንዱዓለም፡-ሆን ተብሎ ሊደረግ አይችልም፡፡ምክንያቱም እኛ ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት ነው ዋናው አለማችን፡፡ ግባችን ለደንበኞቻችን የተሻለ እርካታን ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህን ለማሳካት በምንጥርበት ጊዜ አንድና ሁለት ሰራተኛ ከኩባንያው ዓላማ ውጭ ከተንቀሳቀሱ ተገቢነት የለውም፤ ኩባንያውንም አይወክሉም፡፡ ሆን ተብሎ የሚደረግ አይኖርም፡፡
አንዳንድ ድርጅቶች በራሳቸው አጠቃቀም ችግር ምክንያት አገልግሎት የማይሰጥበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ለምሳሌ ለ10 ሺ ሰዎች አገልግሎት የመስጠት አቅም ያለው ዋይፋይ 11ሺ ሰው የሚጠቀምበት ከሆነ ኔት ወርኩ ስለሚጨናነቅ መዘግየት ይፈጠራል፡፡ ይህ ከራስ አጠቃቀም ጋር ይያያዛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የጸጥታና የተለያዩ ችግሮች ሲከሰቱ የኢንተርኔት አገልግሎት የሚቋረጠው ለምንድን ነው?
ዶክተር አንዱዓለም፡-ኢትዮ ቴሌኮም ኢንተርኔት በመክፈትና በመዝጋት ሂደት ውስጥ አይገባም፡፡ መንግስት የራሱ አደረጃጀት አለው፡፡ ከተለያየ አቅጣጫ አንጻር የማቋረጥ እርምጃ ሊወስድ ይችላል፡፡
አዲስ ዘመን፡-በዓለም አቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ህብረት ተሸላሚ ሆናችኋል፡፡ ይህ ሽልማት ከአገልግሎታችሁ አንጻር ተገቢነት አለው የሚል እምነት አለዎት?
ዶክተር አንዱዓለም፡-በአሁኑ ጊዜ ተቋሙ በፈጣን ዕድገት ላይ ነው፡፡ ከነበረበት የደንበኞች እሮሮና አቤቱታ ራሱን አላቋል፡፡ የደንበኞች ተጨማሪ አገልግሎት  የመፈለግ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ አገልግሎቱ ከበፊቱ በእጅጉ ተሻሽሏል፡፡ ከወረቀት ነጻ የሆነ ዘመናዊ ሥርዓት በመዘርጋት አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ አንድ የዓለም አቀፍ ተቋም ባጠናው ጥናት መሰረት ኢትዮ ቴሌኮም በኔት ወርክ አቅሙና በግዝፈቱ ከአፍሪካ አንደኛ፤ በዓለም ደግሞ 31ኛ ነው፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም የሰበሰበውን ገንዘብ ለአገር ልማት ነው የሚያውለው፡፡ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት እንዲውል ነው የሚያደርገው፡፡ ሽልማቱ በፍጥነት ማደጋችንን፣ ዘመናዊ አሰራር መተግበራችንና ለማህበረሰቡ የምናደርጋቸውን አስተዋጽኦዎች ግምት ውስጥ ያስገቡ ናቸው፡፡
ተቋሙ እስካሁን ድረስ በአስራዎች የሚቆጠሩ ሽልማቶችን ተቀብሏል፡፡ በአፍሪካ፣ በአውሮፓና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሽልማቶች ተሰጥተውታል፡፡ ይህ ግን ኢትዮ ቴሌኮም የተጨበጨበለትና የደንበኞችን እርካታ ጥግ ያደረሰ ነው የሚል ትርጓሜ የሚያሰጥ አይደለም፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ክፍተቶች አያጋጥሙም ብሎ መውሰድ ስህተት ነው፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በሌሎች ተቋማት አማካኝነት ለዘጠኝ ዙር ያህል የደንበኞች እርካታ ጥናት ተካሄዷል፡፡ በክልሎችም ሆነ በአዲስ አበባ ደንበኞች በተቋሙ አገልግሎት ጥሩ እርካታ እንዳላቸው ነው ጥናቱ የሚያመላክተው፡፡ እርካታውን ለማሳደግ አሁንም ብዙ መስራት አለብን፡፡
አዲስ ዘመን፡-ኢትዮ ቴሌኮም በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ አቻ ኩባንያዎች ጋር የመወዳደር ብቃት አለው ብለው ያምናሉ?
ዶክተር አንዱዓለም፡- በአሁኑ ጊዜ ከየትኛውም ዓለም አቀፍ ኩባንያ ጋር ለመወዳደር የሚያስችለው አቅም፣ አደረጃጀትና የሰው ኃይል እንዳለው በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡ አገልግሎቱን ከአገር ውጭ ለመስጠት ዕቅድ ይዘናል፡፡ በየትኛው በኩል ብንገባ ተወዳዳሪ እንሆናለን በሚል የጎረቤት አገሮችን ደካማና ጠንካራ ጎን እያጠናን ነው፡፡ መንግስት ለቴሌኮም መሰረተ ልማት በከፍተኛ ደረጃ ኢንቨስት ያደረገው አገልግሎቱን ለህብረተሰቡ ለማዳረስ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ ጭምር ነው፡፡ ውድድር ቢኖር እንኳ ኢትዮ ቴሌኮም በዚህ ልክ ተዘጋጅቷል ብዬ ነው የማስበው፡፡
ከአገር ውጭ ኢንቨስት ለማድረግ ዓለም አቀፍ የንግድ ክፍል አቋቁመናል፡፡ ለመወዳደር የሚያስችል አደረጃጀትና ተቋም ፈጥረናል፡፡ በተከታታይ ሰራተኞቻችን የምናሰለጥንበት የቴሌኮም ማሰልጠኛ አካዳሚ አለን፡፡ለሁሉም ተማሪዎች ክፍት ከመሆኑም በላይ ከሌሎች አፍሪካ አገሮች የሚመጡም የሚሰለጥኑበት ነው፡፡ ተወዳድረን ለማሸነፍ የምንችልበት አደረጃጀት፣ የሰው ኃይል አቅምና ቴክኖሎጂ እየፈጠርን ነው፡፡እኛ አገር አገልግሎቱን ብቻችንን የምንሰጥ ቢሆንም ከአቻ ተቋማት ጋር እየተወዳደርን ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ እነ ቫይበር፣ ዋትስ አፕና ዊቻትን የመሳሰሉት ደርምሰውን ገብተዋል፡፡ እዚህ ገብተው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጡ ናቸው፡፡ በድርድርም ሆነ በቴክኖሎጂ ከእነሱ በልጠን ገቢ መካፈል አለብን፡፡ ግማሹ እየሰረቀን ግማሹ ደግሞ በቴክኖሎጂ አዳዲስ ነገሮችን ይዞ እየመጣ ነው፡፡ ስለዚህ ተቋማችን ተወዳዳሪ መሆን ይችላል፡፡ የእኛ መሀንዲሶች አውሮፓና አሜሪካ እየሄዱ ነው የሚሰሩት፡፡
አዲስ ዘመን፡-ኢትዮ ቴሌኮምና ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከመንገዶች ባለስልጣን ጋር ተናበው ባለመስራታቸው በተለይም የእግረኛ መንገዶች በየጊዜው ሲቆፈሩ ይስተዋላል፡፡ በዚህም የአገር ሀብት ከመባከኑም በላይ ሰዎች ጉድጓድ ውስጥ እየገቡ ህይወታቸው የሚያልፍበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ያደረጋችሁት ጥረት አለ?
ዶክተር አንዱዓለም፡-ይህ ችግር መስተዋሉ እውነት ነው፡፡ እኛም እንደ ተቋም የሚያሳስበንና የሚቆጨን ጉዳይ ነው፡፡ በጋራ አቅዶና ተቀናጅቶ ብዙ ገንዘብ ማዳን ሲቻል ሁሉም በራሱ መንገድ ሲጓዝ፤ አንዱ በጀት ሳይፈቀድለት ወደ ኋላ ሲጎተት፤ ሌላው የቆፈረውን መልሶ ሲቆፍረው ጉድጓዱ ሳይከደን ቀርቶ የሰው ህይወት ሲጠፋ ማየት ያሳዝናል፡፡
አሁን መሰረተ ልማቶችን የሚያቀናጅ ኤጀንሲ ተቋቁሟል፡፡ መንገድ፣ ኤሌክትሪክ፣ ውሃና ፍሳሽ፣ ኢትዮ ቴሌኮምና ባቡር ኮርፖሬሽን ተቀናጅተን እንድንሰራ የሚያስችል ነው፡፡ አሁን ሁሉም በየፊናው መቆፈር አይችልም፡፡ ለምሳሌ አሁን እኛ መንገዶች ካልፈቀደልን እንደፈለግን መንገድ መቁረጥ አንችልም፡፡ መንገድ ሲሰራ በጀት እንሰጥና የእኛም ስራ አብሮ ይሰራል፡፡ ከበፊቱ ብዙ ለውጥ ቢኖርም የሚፈለገው ደረጃ ላይ ግን አልተደረሰም፡፡
አዲስ ዘመን፡-ባለፉት ስድስት ወራት ኢትዮ ቴሌኮም ምን ያህል ገቢ አገኘ?
ዶክተር አንዱዓለም፡-ባለፉት ስድስት ወራት ዕቅዳችን 19 ቢሊዮን ብር ቢሆንም 18 ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘት ችለናል፡፡የዓመቱ ዕቅዳችን 38 ቢሊዮን ብር ሲሆን ዕቅዱን ለማሳካት ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያለነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ፈተናዎች ምንድን ናቸው?
ዶክተር አንዱዓለም፡- ብዙ ፈተናዎች ያጋጥሙታል፡፡ የቴሌ ኮም ማጭበርበር ትልቁ ፈተና ሆኖብናል፡፡ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመጣመር እርምጃ እየወሰድን ነው፡፡ ትልቅ የውጭ ምንዛሬ እያስገኝ ያለ ተቋም ነው፡፡ ይህንን ነው የሚሻሙብን፡፡ ስለዚህ የመቆጣጠር ስራ ብንሰራም የቴሌኮም ማጭበርበር አሁንም ፈተናችን ስለሆነ በተከታታይነት መስራት አለብን ፡፡
ሌላው ችግር ደግሞ በመሰረተ ልማቶቻችን ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ናቸው፡፡ ከስምንት ሺ በላይ ታዎሮች አሉን፡፡ መሬት ላይ የተቀበረ ፋይበር ኬብል አለ፡፡ ይህን ሆን ብለው ወይም ሳያውቁ የሚቆርጡ አሉ፡፡ለመጠገንም ጊዜ ይወስዳል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥም ሌላው ፈተናችን ነው፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ከ80 በመቶና በክልሎች ደግሞ ከ60 በመቶ በላይ መጠባበቂያ ጄኔሬተሮች አሉን፡፡ ለጄኔሬተሮች ነዳጅ ለመሙላትና ለጥገና ብዙ ወጪ ያስፈልጋል፡፡ ጄኔሬተሮቹ ኤሌክትሪክ ሲጠፋ አገልግሎቱን እንዳይቋረጥ ወሳኝ ናቸው፡፡
በዓለም ላይ ቴክኖሎጂው እየተለዋወጠ መምጣቱን ተከትሎ ቴሌኮም ገቢውን በከፍተኛ ደረጃ እያጣ ነው፡፡ አሁን ወደ አምስተኛው ትውልድ እየሄደ ነው፡፡አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማምጣት ካልተቻለ በዘልማዳዊ ቴሌኮም መምራት አይቻልም፡፡ ዛሬ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ቤታቸው ቁጭ ብለው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር ደርምሰው ሊገቡ ይችላሉ፡፡ እናም ኢንዱስትሪው የቴክኖሎጂ ፈተና አለበት፡፡ በሌላ በኩልም የግዥው ጉዳይ በውጭ ምንዛሬ ምክንያት ፈተና ሆኖብናል፡፡ አንዳንድ ግዥዎቻችን ቆመዋል፡፡ ችግሩ ጊዜያዊ ቢሆንም ትልቅ ፈተና ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡-የሞባይል ስልክ ታሪፍ ተመጣጣኝ አይደለም የሚሉ ወገኖች አሉ?
ዶክተር አንዱዓለም፡- በዚህ ሀሳብ አልስማማም፡፡ በሞባይል ስልክ የዳታና የድምፅ አገልግሎት ነው የምንሰጠው፡፡ የድምፅ ታሪፍ ዋጋው ከምስራቅ አፍሪካ ዝቅተኛው ነው፡፡የዳታውም ቢሆን ከፍተኛ የሚባል አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን፡-ለ2ጂና ለ4ጂ የሚከፈለው ዋጋ ተመሳሳይ ነው?
ዶክተር አንዱዓለም፡- የዋጋ ልዩነት የላቸውም፡፡ 4ጂ እጅግ በጣም ፈጣን ነው፡፡ የሚከፈለው በወረደው ዳታ ልክ ነው፡፡ በ2ጂ መረጃ ለማውረድ የሚደረገው ጥረት ቀርፋፋ ነው፡፡ 2ጂ ሁለት ደቂቃ ሲወስድ 4ጂ 10 ሰከንድ ሲፈጅ ይችላል፡፡ ስለዚህ ጊዜን ይቆጥባል፡፡ ሁለቱም ግን ተመሳሳይ መፅሀፍ ነው ያወረዱት፡፡ ነገር ግን ሰው ጊዜና ዳታውን ሳይሆን ቆይታውንና ገንዘቡን ብቻ ነው የሚለካው፡፡
አዲስ ዘመን፡-የኢትዮ ቴሌኮም ቀጣይ ዕቅድ ምንድን ነው?
ዶክተር አንዱዓለም፡-ከአገር ውጭ አገልግሎት ለመስጠት ዕቅድ ይዘናል፡፡ማስፋፊያ ካደረግን ስምንት ዓመት ሊሞላው ነው፡፡ ጥናት በማካሄድ ማሻሻያዎች ለማድረግም ሀሳቡ አለ፡፡ ፍላጎትን መሰረት ያደረገ የማስፋፊያ መርሀ ግብርም ይኖረናል፡፡ በእነዚህ ማስፋፊያዎች ራሱን የቻለ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡
እስካሁን የተሰራው ሰውና ሰውን በስልክ ማገናኘት ነው፡፡ አሁን ግን ዓለም ሰውና ዕቃን፣ ዕቃና ዕቃን ማገኛነትን ነው እየሰራ ያለው፡፡ ለምሳሌ ቢሮ ሆነህ ቤትህ ላለ ዕቃ ደውለህ መልስ ይሰጥሀል፡፡ ፍሪጅህ ጋ ደውለህ ስንት እንቁላል ውስጡ እንዳለ ይነግርሀል፡፡ ይህን አገልግሎት የመስጠት ሀሳቡ አለን፡፡
በእኛ አገር አብዛኛው ህብረተሰብ ስልኩን ለመደወል፣ ኢሜልና መልዕክት ለመላላክ ነው የሚጠቀምበት፡፡ ከዚህ የዘለለ አገልግሎት መስጠት ይቻላል፡፡ በጤና፣ በግብርና፣ በትምህርትና በመዝናኛ ዘርፍም አገልግሎት መስጠት ይኖርብናል፡፡
አዲስ ዘመን፡-አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር አንዱዓለም፡-እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ጌትነት ምህረቴ

Published in ኢኮኖሚ

የደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ናሽናል ኮንግሬስ (ኤ ኤን ሲ) ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች በፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ ልባቸው ክፉኛ ቆስሏል። ምናልባትም ፓርቲው ከትናንት እስከ ዛሬ በነበሩት መሪዎች ይህን አይነት ቅሌት አስተናግዶ አያውቅም ይሆናል።በተለይ ደግሞ ከሙስና ጋር ተያይዞ ሲታይ እአአ በ2016 ብቻ 18 የሙስና ክሶች የቀረበበት የፓርቲው አባል የለም። የዚህ አይነቱ የክስ ታሪክ ባለቤት የሆኑት የደቡብ አፍሪካው መሪ ጃኮብ ዙማ ብቻ መሆናቸው ነው የሚነገረው፡፡
ጃኮብ ዙማ በሙስና ቅሌት ብቻ ሳይሆን አስገድዶ በመድፈር ወንጀልም ጭምር ተከሰው ፍርድ ቤት ቀርበዋል። ይህን አይነቱ ድርጊት መደጋገሙን ተከትሎ ፕሬዚዳንቱ በኤ ኤን ሲ ፓርቲ አባላት ጥርስ ተነክሶባቸዋል። ለዚህም የመጀመሪያውን እርምጃ በፈረንጆቹ ወርሃ ታህሳስ 2017 ሰውዬውን ከፓርቲው መሪነት በማንሳት በሌላ ሰው ለመተካት የሚያስችል አጋጣሚን ፈጠሩ።
ፓርቲውን መምራት የሚችል ሰው ለመምረጥ የሚያስችል ድምጽ እንዲሰጥ ተደረገ። ለኤ ኤን ሲ ፓርቲ መሪነት ሁለት ዕጩዎች በተፎካካሪነት ቀረቡ፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሲሪል ራማፎሳ እና ሰፊ የዲፕሎማሲ ተሞክሮ ያላቸው እና ባንድ ወቅት የፕሬዚዳንቱ ባለቤት የነበሩት ዶክተር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ። በመጨረሻም ራማፎሳ ተመርጠው የፓርቲውን የመሪነት በትረ ሥልጣን ተረከቡ፡፡ ፓርቲው በስልጣን ላይ ያሉትን ዙማን እንደማይመርጥ ቀደም ብሎ ቢገመትም ከፓርቲው ይታገዳሉ የሚል እምነት አልነበረም፡፡ ግን እንዳልተጠበቀ ሆኖ አለፈ፡፡
ፓርቲያቸው ጀርባውን ያዞረባቸው ዙማ፤ በደቡብ አፍሪቃውያን ጭምርም የመገፋታቸው እውነታ የሚያሳዩ ምልክቶች መታየት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ ተቃውሞው የፕሬዚዳንቱን ቀጣይ ዕጣ ፈንታን ማመላከቱም አልቀረም፡፡ በተለይም የሥልጣን ዘመናቸው አንድ ዓመት ቢቀረውም ከወዲሁ ስልጣናቸውን ይልቀቁ የሚሉ ጥያቄዎች እና ጫናዎች መብዛታቸው የሰውዬውን ያለመፈለግ እውነታ እያሳዩ ነው፡፡
ከፈረንጆቹ 2009 ጀምሮ በርዕሰ ብሄርነት የቆዩት ዙማ ስልጣን እኤአ በ2019 እስከሚካሄደው ምርጫ ይቆያሉ። ይሁንና በደቡብ አፍሪካ የሚነፍሰው ንፋስ ዙማ ስልጣናቸውን ቀድመው እንዲያስረክቡ የሚያስገድድ ነው።
ዙማ በ17 ዓመታቸው የአፍሪካ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል ሆኑ፡፡ እአአ በ1962 ኡምክሆንቶ ዌ ሲዝዌ የተባለውን ወታደራዊ ክንፍ ተቀላቀሉ። ደቡብ አፍሪካን ከአፓርታይድ ቀንበር በማውጣት ነጻዋን ምድር ለመመስረት ነፍጥ አነሱ። ከደቡብ አፍሪካዊያን እና የጥቁር መመኪያ ከሆኑት ከእነ ኔልሰን ማንዴላ ጋር አብረው ቆሙ። የደቡብ አፍሪካውያንን ሰቆቃ ለማስቆም፤ ደም መፍሰሱን ለማስቀረትና የህዝቡን እንባ ለማበስ መሳሪያ አንግበው ወደ ፍልሚያ ገቡ። በመሳሪያ ፍልሚያው ግን ዕድል ከእሳቸው ጋር አልነበረችም። በ1963 ከ45 ምልምሎች ጋር ተያዙ፡፡ በመንግስት ግልበጣ ሙከራ ተይዘው ከእነ ኔልሰን ማንዴላ ጋር ሮቢን ደሴት ሆነ ማረፊያቸው። ወደ ጨለማው እስር ቤትም ተወረወሩ፤ ለአስር አመታት በዛው መቆየት ዕጣ ፈንታቸው ሆነ።
የኔልሰን ማንዴላ ትግል ድል አድርጎ ብቅ ሲል፤ ዙማም አብረው ታዩ። በፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ የስልጣን ዘመን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በመሆን ተሾሙ። ከዚያም በፕሬዚዳንት ታምቦ ምቤኪ ዘመን የሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን የመሪነቱን ጉዞ ቀጠሉ። እኤአ በ2005 ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን የስልጣን ጫፍ ለመድረስ ያላቸውን ፍላጎት ለማሳካት የበለጠ ተጠጉ። ጃኮብ ዙማ የርዕሰ ብሄርነቱን ስልጣን በ2009 ምርጫ ለመጨበጥ ቻሉ። በፓርቲያቸውም ሆነ በህዝቡ ዘንድ ተወዳጅ ነበሩ፡፡ በዚህም በ2015 ለሁለተኛ ጊዜ የፕሬዚዳንትነት ምርጫውን ለማሸነፍ ችለዋል፡፡
ሆኖም ግን በሂደት ከምክትል ፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው ጀምሮ ሲታሙበት የነበረው የሙስና ክስ እያገለገሉ ሰውዬውን ከተወዳጅነት መንበራቸው ሊያስለቅቃቸው ማንገራገጭ ጀመረ። ክሶች እየበዙ በመምጣታቸው ፕሬዚዳንቱ በህዝቡ ዘንድ የነበራቸው እምነትና ፍቅር እየቀነሰ መጣ፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያሽቆለቁል አድርገዋል የሚል ትችት ክፉኛ ይሰነዘርባቸው ጀመር፡፡
በተለይ በ2016 እና 17 ለደቡብ አፍሪካዊያን ጥሩ ጊዜ የሚባል እንዳልሆነ በርካቶች ይናገራሉ።የአገሪቱ ኢኮኖሚ በአንድም ሆነ በሌላም ምክንያት ተዳክሟል። በአገሪቱ ከፍተኛ የሆነ ስራ አጥነት ተንሰራፍቷል። ኢሊኖ ባስከተለው ድርቅ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የሚኖሩ ደቡብ አፍሪካዊያን ከባድ የረሃብ አለንጋ አርፎባቸዋል። ይሄም ሁኔታ ጃኮብ ዙማ ቆይታቸውን ከምንም በላይ በህዝብ እንዳይፈለግ አድርጎታል። ስልጣናቸውን ካለጊዜያቸው እንዲለቁ ግፊቶች የማሳደሩ ምክንያት ተደርጎ ይነሳል።
ባለፈው ዓመት በደቡብ አፍሪካ የታየውና ብዙዎችን ያስደነገጠው የመጤ ጠል ግጭትና ሁከትም ዙማን ለትችት መዳረጉ አልቀረም፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ቢቀዛቀዝም የእርሳቸው ሙሰኝነት ገዝፎ መታየቱ ሌላው ምክንያት ሆኗል። በተደጋጋሚም የሙስና ክሶች እየቀረቡባቸው በፓርቲውም እስከ መከሰስ ደርሰዋል፡፡ በአንድ ወቅት ዙማ በማጭበርበር፣ በሙስና፣ በህገወጥ ገንዘብ ማዘዋወርና በመሳሰሉት በድምሩ ወደ 700 የሚሆኑ ክሶች እንደቀረቡባቸው ነው የሚነገረው። ምንም እንኳን ክሶቹ ቢነሱላቸውም፡፡ ከእነዚህ ክሶች ሁሉ ግን የደቡብ አፍሪካዊያንን ልብ በቁጣ ያሸበረው የግል የመኖሪያ ቤታቸው እደሳ ጉዳይ ነው፡፡ ስልጣናቸውን በመጠቀም መኖሪያቸውን በከፍተኛ ገንዘብ በማሳደስ ህዝቡን ለቅሬታ ዳረጉት።
ለእደሳው አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዶላር ይበቃል ቢባልም ተጨማሪ እንዲወጣ አደረጉ፡፡ በዚህ ሳያበቃም 20 ሚሊዮን ዶላር ከመንግስት ካዝና በማውጣት ለእድሳቱ እንዲውል ፈቀዱ።ይሄም ደቡብ አፍሪካዊያንን አስቆጣ። ፍርድ ቤት ቀርበውም ጉዳያቸው ታየ፡፡ የደቡብ አፍሪካው ህገ መንግስታዊ ፍርድ ቤት፣ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ፣ የግል መኖሪያ ቤታቸውን ለማደስ ያለ አግባብ ከተጠቀሙበት ገንዘብ ውስጥ 16 ሚሊዮን ዶላር ያህሉን እንዲመልሱ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡
አፓርታይድን ለማስቀረት የታገሉት ጃኮብ ዙማ፤ መሰረቱን ህንድ ከሚያደርገው ጉፕታ ቤተሰብ ጋር የፈጠሩት ያልተገባ ግንኙነት ሌላው የሚወቀሱበት ጉዳይ ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካ በኮምፒውተር የንግድ ዘርፍ ሥራ የጀመረው የህንዳዊያኑ ባለሀብቶች ድርጅት በአገሪቱ የሚኒስቴሮች ሹም ሽር ላይ ሳይቀር ረጅም እጅ እንዳለው ይታማል፡፡ ተፅዕኖ ፈጣሪነቱም ከፍተኛ ነው ይባላል፡፡ ዙማ ከባለሃብቶቹ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ተጠቅመው የተለየ ጥቅም ያገኛሉ በሚል የሃገሪቱ አቃቤ ህግ ጉዳዩን እያጣራ ይገኛል፡፡ ፕሬዚዳንቱና የጉፕታ ቤተሰብ አባላት ክሱን ቢያስተባብሉም እውነታውን ግን መሸፋፈን አልቻሉም ነው የተባለው፡፡ ቅሬታው በርትቶ የፕሬዚዳንቱ ወንበር እየተነቀነቀ ነው፡፡ የሥልጣን ዘመናቸውን ሳያጠናቅቁ ‹‹በቃዎት››እየተባሉ ነው፡፡
አልጀዚራ ይዞት በወጣው ዘገባ፤ በፓርቲው ውስጥ ያለው የሃይል ፍጥጫ በመጪው ዓመት ከሚደረገው ምርጫ ቀደም ብሎ ፓርቲውን ለሁለት ከመክፈሉ በፊት ችግሩ እንዲፈታ የፓርቲው አባላት ይፈልጋሉ። በመሆኑም ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማን ከስልጣን ለማውረድ ጥረት ተጀምሯል፡፡
እንደ ኒውስ 24 ዘገባ ከሆነ ደግሞ በአፓርታይድ ትግል ወቅት ታጋይ የነበሩት እና በአንድ ወቅት ታስረው የነበሩት ፕሬዚዳንት ዙማ ባለፈው እሁድ ከፓርቲው ስድስት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ቢወያዩም ከስልጣን እንዲወርዱ የቀረበላቸውን ሃሳብ አልተቀበሉትም። በእለቱ ሁለት ሰዓታት የፈጀ ክርክር ካካሄዱ በኋላ ዙማ ስልጣን እንዲያስረክቡ ቢጠየቁም በስልጣን የመቆየት ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡ «ህዝቡ አሁንም ድረስ ይወደኛል»ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ይህን ተከትሎም ጫና ውስጥ እያሉም ስልጣናቸውን ለማስረከብ ፍላጎት የሌላቸው ናቸው የሚሉ አስተያየቶችም እየተሰነዘሩ ነው፡፡
ሰኞ ዕለት ከፍተኛ ፖለቲከኞች በዙማ ዕጣ ፈንታ ላይ ለመምከር አስቸኳይ ስብሰባ በጆሃንስበርግ ማካሄዳቸውን ጠቅሶ፤ፕሬዚዳንቱ በሙስና መወንጀላቸውን ተከትሎ ከስልጣን እንዲለቁ የቀረበላቸውን ጥያቄ ውድቅ ማድረጋቸውን የዘገበው ደግሞ ሜል ኦላይን ነው፡፡ ይህን ተከትሎም በደቡብ አፍሪካ የሚሰማው የተቃውሞ ጩኸት አይሎ ታይቷል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሥልጣን ይልቀቁ የሚለው ድምፅ በደቡብ አፍሪካ ጎልቶ እየተሰማ ነው፡፡
ቢቢሲ ባወጣው ዘገባ ፤ሰኞ የነበረው ስብሰባ ፕሬዚዳንት ዙማን ከስልጣን የማውረድ አጀንዳ እንዳልነበር የፓርቲው ቃል አቀባይ መግለጻቸውን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል። ማክሰኞ የፓርቲው ብሄራዊ ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰበሰበ ሲሆን ፕሬዚዳንት ዙማ ሐሙስ መግለጫ እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡ አንዳንዶች ከዚህ መግለጫ በፊት ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን እንዲለቁ ይፈልጋሉ። በማዕከላዊ ኮሚቴው ጥሪ ቀርቦላቸው አሻፈረኝ ካሉም በፓርላማው የመተማመኛ ድምጽ ሊሰጥባቸው እንደሚችል ዘገባው አመልክቷል፡፡
በርካታ ደቡብ አፍሪካዊያን አደባባይ በመውጣት ጃኮብ ዙማ ስልጣን እንዲለቁ የተቃውሞ ድምፃቸውን ማሰማቱን ቀጥለዋል። ጃኮብ ዙማ መንበረ ሥልጣናቸውን ከለቀቁ ባለፈው ታህሳስ የኤ ኤን ሲ ፓርቲ መሪ በመሆን የተመረጡት ሲሪል ራማፎሳ ቦታውን እንደሚይዙ ይጠበቃል፡፡ በተቃውሞው ይሄው ሃሳብ እየተንፀባረቀ ይገኛል፡፡ አሁን እየታየ ያለው ከፍተኛ ተቃውሞ የደቡብ አፍሪካን መጻኢ ዕድል ወደ ሁከትና ብጥብጥ እንዳያመራው ተሰግቷል፡፡

ዳንኤል ዘነበ

Published in ዓለም አቀፍ
Wednesday, 07 February 2018 16:57

በሠላም ውሎ ይደር መንደሩ

ፊቱ መከፋቱን ያሳብቅበታል፡፡ አንዳች ነገር ገብቶታል፡፡ የመከፋቱ ምክንያት ባይታወቅም ፤ለመከፋቱ ግን እርግጠኛ ነኝ፡፡ ከአጠገቡ የተቀመጠው ጓደኛ የማፅናኛ ቃላትን ቢያዥጎደጉድም ያመጣው ውጤት የለም፡፡ መቆዘምና መተከዝ ብቻ፡፡ በአንድ በኩል ቁዘማው በሌላ ጎኑ ደግሞ የማረጋጋት ጥረቱ ቀጥሏል፡፡ ለተወሰነ ደቂቃ አርምሞ ሰፈነ፡፡ ‹‹የየታክሲው ረዳት ወራጅ አለ?›› ሲል ጓደኛሞች ከራሳቸው ዓለም ተመለሱ፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሆናቸውን ከጫወታቸው ተረድቻለሁ፡፡ አራት ኪሎ ሥላሴ አካባቢ ከታክሲ አብረው ቢወርዱም መንገዳቸው ለየቅል ነበር፡፡ አንዱ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሌላኛው ወደ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን፡፡ ከታክሲ ሳይወርዱ ነበር እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት፡፡ የተከፋው ወጣት ‹‹ትንሽ ለመረጋጋት ቤተ ክርስቲያን ገብቼ እመጣለሁ›› በማለት ለጓደኛው ነግሮታል፡፡
ብዙዎች ሲያደርጉ አይቻለሁ፤ሰምቻለሁ፡፡ ሲረበሹና ሲከፉ ቤተ እምነትን ምርጫቸው የሚያደርጉ በርካታ ናቸው፡፡ የዩኒቨርሲቲው ተማሪ ያረጋገጠልኝም ይህንኑ እውነታ ነው፡፡ ሁሉም እንደ እምነቱ ወደ ሚፈልገው ቤተ እምነት ያቀናል፡፡ ያስጨነቀውንና የረበሸውን ጉዳይ ለመርሳት፡፡ ቤተ እምነቶች በሠላም ፈላጊዎች ዋናዎቹ ተመራጭ ቦታዎች ናቸው፡፡ የተረበሸ፣ የተጨነቀ፣የተቸገረና ያለመው እንዲሳካላት የፈለገ ሁሉ እንደ ሃይማኖቱ ቤተ እምነቶችን መጎብኘቱ አይቀርም፡፡ ተማሪውም ጭንቀቱን ለማራገፍ የመረጠው ይህንኑ ቦታ ነው፡፡
ለሠላም እጅጉን ተመራጭ የሆኑ ቤተ እምነቶች ሠላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ድርሻቸው በጣሙን የጎላ ነው፡፡ ለዚህም ነው የሃይማኖት ተቋማት ሠላምንን የማረጋገጫ ቁልፍ መሳሪያዎች ናቸው የሚባለው፡፡ ህዝብ ለሠላም ዘብ እንዲቆምና ፀረ ሠላም ድርጊቶችን እንዲከላከል በማድረግ ረገድ የሃይማኖት ተቋማት ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፤ግዴታቸውም ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ግልፅ ነው፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ ሁሉም ሃይማኖቶች ስለ ሠላም ነው የሚሰብኩት፡፡ ከሠላም በተቃራኒ የቆመ ሃይማኖት እንደሌለ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡
ሠላምን አጀንዳው ያላደረገ ፤አስተምህሮውም ከዚህ የተጣላ ሃይማኖት ይኖራል ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡ በአገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት የተለያየ ምክንያትን መነሻ ያደረጉ ግጭቶች ተከስተዋል፡፡ በህይወትና ንብረትና ላይም ከባድ ጉዳትን አስከትለዋል፡፡ በውጤቱም ታሪክ አይሽሬ ጥቁር አሻራን ጥለው አልፈዋል፡፡ በርካታ አገር ተረካቢ ወጣቶች ተቀጥፈዋል፤ለማይድን የአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ የአገርን ዕድገት ለማፋጠን የሚረዱ መሰረተ ልማቶች ወድመዋል፡፡
እነዚህን ጉዳቶች ዞር ብለን ስንመለከት የሠላም ዋጋው ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ሠላምን ሳይታጠቁ ማቀድም፣ ማልማትም፣ ማለምም ትርፉ ምንም ከመሆን አይዘልም፡፡ እናም ሁሌም ስለ ሠላም መዘመርና መስበክ የሁሉም የየቀኑ አጀንዳ ሊሆን ይገባል፡፡ ያለ ሠላም ምንም ማድረግና የትም መድረስ አይቻልምና፡፡ በዚህ በኩል ታዲያ የሃይማኖት አባቶች ከፍተኛ ሚና አለባቸው፡፡ ለአማኙ ምዕመን በየቤተ እምነታቸው ማስተማርና መስበክ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከመስመር ያለፉትንም መምከርና መገሰፅ አለባቸው፡፡ ይህ ሃይማኖታዊ ግዴታቸውም ጭምር ነው፡፡
የሃይማኖት ተቋማቱን በአንድ ጣሪያ ሥር የሚያሰባስብ ጉባዔ አለ፡፡ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ፡፡ ይህም ሁሉንም ሃይማኖቶች በማሰባሰብ በተለይም በሠላም አስተምህሮ ዙርያ በስፋት የሚንቀሳቀሱበትን ዕድል ፈጥሯል፡፡ የሠላም አስተምህሮን ዋናውና ቀዳሚው አጀንዳቸው አድርገው እንዲጓዙ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል፡፡ በቅርቡ የሃይማኖት መሪዎቹ በኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን በተዘጋጀ መድረክ ላይ የሠላምን አስፈላጊነት አበክረው ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ የሃይማኖት አባቶቹ በሠላም ዙርያ የሚጠበቅባቸውን የቤት ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ወሰን አካባቢ የተከሰቱ ግጭቶችን ለማረጋጋት የሄዱበትንም ጥረት ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡ ይህ ተግባር የሚበረታታና የሚደነቅ ነው፡፡ እንደ ሃይማኖት ተቋምም ይጠበቅባቸዋል፡፡
ሁሉም ሃይማኖቶችም ለሠላም ቅድሚያ ከመስጠት ያለፈ አጀንዳ እንደሌላቸው ነው የመሰከሩት፡፡ ሠላምን በማደፍረስ የሚገኝ አንዳች ውጤትም፣ ትርፍም አለመኖሩን በአፅንዖት ገልፀዋል፡፡ የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ የሆነ ሰው ከሠላም ያፈነገጠ ተግባርን ማከናወን እንደማይጠበቅበትም ነው የተወሳው፡፡ በፀረ ሠላም ድርጊት ላይ የተሰማራ ሰው ከሃይማኖቱ ህግጋትና አስተምህሮ ያፈነገጠ በመሆኑም ተቀባይነት የለም ሲሉ ተደምጧል፡፡ የሃይማኖት ተከታይነቱ ከስም ያለፈ አለመሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡ የአንድ ሃይማኖት ተከታይ መልካም ሥነ ምግባር መገለጫዎች መካከል ሠላም ወዳድነት አንዱ ነው፡፡
የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ በመንፈሳዊ አባቶቹ የተባሉትን ሁሉ ትክክለኛነት ይቀበላል፤ የተባሉት መተግበር እንዳለባቸውም ያምናል፡፡ የሃይማኖት አባቶቹ ሠላም እንዲሰፍን የሚያደርጉትንም ጥረት ያደንቃል፤ያበረታታል፣ይደግፋል፡፡ ግጭት በተከሰቱባቸው አካባቢዎች የሃይማኖት ተቋማቱ በግልና በሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በኩል ላደረጉትና ለሚያደርጉት መንፈሳዊና ቁሳዊ ድጋፍ ትልቅ ክብርና ምስጋና ይሰጣል፡፡ በግጭቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸውን የተፈናቀሉትን መጎብኘትና ማፅናናትም እሰየው የሚያስብልና በቀጣይም ሊጠናከር የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ያምናል፡፡ በግጭቱ ምክንያት መቃቃር ውስጥ የገቡትን ለማስታረቅና የቀደመውን የመተሳሰብ፣የአንድነትና የመረዳዳት ባህል ለመመለስ የሚደረገውን ጥረትም በመልካምነቱና በጠንካራ ጎን የሚነሳ እርምጃ ነው፡፡
ጠንካራ ጎኖቹ በጥንካሬያቸው የሚወሰዱና በቀጣይ እየጎለበቱ የሚሄዱ መሆን እንዳለባቸው እምነቴ ነው፡፡ ምክንያቱም በህዝቦች መካከል መተሳሰብና መከባበር እንዲሰፍን ከሃይማኖት አባቶች በላይ ማንም አይኖርም፡፡ ሃይማኖት የሰውን ልጅ በሚፈለገው መንገድ ለመምራትና በመልካም አስተሳሰብ ለመግዛት ወደር የለውም፡፡ ሁሉም ለሚያምነው ሃይማኖት የመገዛቱ አመለካከት ከፍተኛ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ትክክለኛ አማኝ እስከ ሆነ ድረስ፡፡ በሃይማኖት አስተምህሮ ሰዎች ይለወጣሉ፣ይታዘዛሉ፡፡ በህግጋቶቹም ይገዛሉ፡፡
የሃይማኖት አባቶች ታዲያ እስከ አሁን ከተጓዙትም በላይ መሄድ ይጠበቅባቸዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የሠላም አየር ሊደፈርስ ይችላል፡፡ ይህን ወደ ቀደመው መመለስ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ የሠላም መደፍረስ መንስዔዎችን ማድረቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም መንስዔዎቹን ለይቶ ማድረቅ፤ ህዝቡ የመንስዔው አካል እንዳይሆን መምከርና መጠበቅ ይገባል፡፡ በዚህ በኩል ታዲያ የሃይማኖት አባቶች ብዙ የቤት ሥራ ይጠብቃቸዋል፡፡
ምዕመኑን ከተኩላ የሚጠብቁ የሃይማኖት አባቶች ናቸው፡፡ ስለሆነም የተኩላውን ሴራ ቀድመው ማሸነፍ አለባቸው፡፡ ምዕመኑ በተኩላው ከመወሰዱ በፊት ጎበዝ እረኛ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ እናም ምዕመኑ የሠላምን አስፈላጊነት በደንብ እንዲረዳና በውስጡ እንዲቀበለው በየቤተ ዕምነቶቻቸው ማስተማር አለባቸው፡፡ የሠላም ጉዳይ የአንድ ሰሞን ዘመቻ ባለመሆኑ በተከታታይነት መስራትና መንቀሳቀስ ተገቢ ነው፡፡ ሁሉም ምዕመን የሠላምን ጠቀሜታ በመረዳት ልጆቹን በማስተማር በጥሩ ሥነ ምግባር ታንፀው እንዲያድጉ መጣር አለባቸው፡፡ በዚህ በኩል የሚቀር ሥራ እንዳለ ይሰማኛል፡፡
የሃይማኖት አባቶች በቤተ እምነቶች በሚኖረው መርሀ ግብር ላይ የሠላምን አስፈላጊነት በማስረጃዎች በማስደገፍ ቢያስተምሩ ጥሩ ውጤት ይመጣል የሚል የግል አስተያየት አለኝ፡፡ ይህ ማለት ችግሮች ሲከሰቱ በዛ ሳቢያ የደረሰውን ጉዳት ማስረዳቱ ክፋት ያለው አይመስለኝም፡፡ ቤተሰባችንን፣ጓደኞቻችንንና ዘመዶቻችንን በሠላም እጦት ማጣታችን ሊያስቆጨን እንደሚገባ ማስገንዘብ ይገባል፡፡
‹‹በሠላም ያዋለን በሠላም ያሳድረን›› የማለቱ ምስጢር ከመንፈሳዊውም ከዘመናዊውም የተጣላ አለመሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ይህ ዓረፍተ ነገር ብዙ ጊዜ በተለያዩ ቤተ እምነቶች በተደጋጋሚ ሲነገር ሰምቻለሁ፡፡ ጥልቅ ምስጢርን ያዘለ ነው፡፡ የሠላምን የገዘፈ አስፈላጊነት የተሸከሙ ቃላት ህብር ነው፡፡ ለመዋልም ሆነ ለማደር ሠላም ያስፈልጋል፡፡ ቀን በሠላም የዋለ ምንም ሳይሆን አድሮ ለመገኘት ዋስትናው ቤት መግባቱ ሳይሆን ሠላም ነው፡፡
ለዚህም ነው የሠላም ዋጋው ከፍተኛ ነው መባሉ፡፡ የሠላምን አስፈላጊነት ሁሉም እንደሙያ ው ፣ዕውቀቱና የሥራ ባህርይው ሳይነካው ማለፍ አይሆንለትም ፡፡ ጉዳዩ ሠላም ነዋ፡፡ ሙዚቀኛው፣ ደራሲው፣ተዋናዩ…ስለ ሠላም ሳይዘፍን፣ሳይፅፍና ሳይተውን አያልፍም፡፡ እነዚህ ሁሉ አካላትን የሚያቅፉት ሃይማኖቶች ድርሻ ደግሞ ከባድ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ እናም ከሄዳችሁት ብዙ እጥፍ በላይ መጓዝ አለባችሁ፡፡ ህዝቡ በሠላሙ ጎዳና እንዲጓዝ ፣በሠላሙ በር ገብቶ እንዲወጣ፣በየቀኑ ሠላምን ስበኩ፣ሠላምን ዘምሩ፡፡

ሠላም ዘአማን 

Published in አጀንዳ

የህዝብን ፍላጎት የማርካትና የማረጋገጥ ኃላፊነት በመንግስት ላይ ይወድቃል፡፡ የህዝብ ውክልናን የተቀበለው መንግስት ለወከለው ህዝብ መሰረታዊና ወሳኝ የሆኑ ልማቶችን ማከናወን ይጠበቅበታል፡፡ መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ውሃ፣ ቴሌኮም፣ ጤና ጣቢያ፣ ትምህርት ቤቶችና መሰል ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን በመገንባት ተደራሽ የማድረግ ኃላፊነትም ግዴታም አለበት፡፡
ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥና የአገሪቱን ዕድገት ለማፋጠን የሚረዱ ዕቅዶችን በመንደፍ ለተግባራዊነታቸው ይተጋል፡፡ የኢኮኖሚ ሽግግሩን ለማሳለጥ የታመነባቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ተገንብተው ለአገልግሎት እንዲበቁ መስራትና መንቀሳቀስም ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም፡፡ ለህዝብና ለአገር የሚጠቅሙ ፕሮጀክቶችን መንደፍ፣ መተግበርና አፈፃፀማቸውን መከታተል ግድ ይላል፡፡
መንግስት ለሚያቅዳቸውና ለሚተገብራቸው ልማታዊ ፕሮጀክቶች ገቢ ዋናውና ቁልፍ መሳሪያ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ምንጩ ደግሞ ከአገር ውስጥ በሚሰበሰብ የግብር ገቢ ላይ ይወድቃል፡፡ ዓመታዊ የአገሪቱ በጀት ሲፀድቅ ከፍተኛው የገቢ ምንጭ ሆኖ የሚቀርበው ግብር ነው፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት ከአገር ውስጥ ታክስ፣ከውጭ ንግድና ቀረጥ ፣ታክስ ካልሆኑ ገቢዎችና ከብሔራዊ ሎተሪ ሽያጭ 199 ነጥብ 11 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ነው የታቀደው፡፡ በስድስት ወራት ታዲያ መሰብሰብ የተቻለው ከ90 ቢሊዮን ብር ብዙም የዘለለ አይደለም፡፡ ይህ አኃዝ ከዓመታዊ ዕቅዱ አንፃር ሲመዘን ከ40 በመቶ በታች ነው፡፡
ለገቢው መቀነስ የግብር ከፋዩ የህግ ተገዥነት ዝቅተኛ መሆን በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡ የቁጥጥር መላላትና የአሰራር ክፍተቶች፣ የግንዛቤ ማነስና የግብር ሥወራም የግብር አሰባሰብ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ እየተስፋፋ የመጣው ኮንትሮባንድ የግብር ትልቅ ፈተና ሆኗል፡፡ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ብቻ 436 ነጥብ 74 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ዕቃዎች በኮንትሮባንድ ወደ አገር ውስጥ ሊገቡና ወደ ውጭ ሊወጡ ሲሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተመልክቷል፡፡ ይህን ህገ ወጥ ድርጊት መግታት ካልተቻለ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ጫና ከባድ ነው፡፡
ብራዚል በየዓመቱ ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ ጎረቤት ኬንያ ደግሞ 70 ቢሊዮን ሽልንግ የሚጠጋ ገንዘብ በኮንትሮባንድ ያጣሉ፡፡ ኢትዮጵያም የፀረ ኮንትሮባንድ ዘመቻውን ካላጠናከረች የእነዚህ አገራት ፈለግ ላለመከተሏ ማስተማመኛ አይኖርም፡፡ ኮንትሮባንድ ከመቀነስ ይልቅ በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱ የችግሩን አሳሳቢነት ከፍ ያደርገዋል፡፡
ኮንትሮባንድ ከግብር የሚገኘውን ገቢ ከማሳነስም በላይ ህገ ወጥነት እንዲሰራፋ ያደርጋል፡፡ ኢኮኖሚን ያቀጭጫል፤ ፍትሃዊ የንግድ ውድድር እንዳይኖር ያደርጋል፤ የህጋዊ ነጋዴዎችን ህልውና በመፈታተን ህገ ወጥነት እንዲንሰራፋ ዕድል ይሰጣል፡፡ በአገር ደህንነት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ጫና ቀላል አይደለም፡፡ ኮንትሮባንድ ክንዱን ሲያበረታ የተገነባውን የግብር ሥርዓት ያፈርሳል፡፡
ይህን የአገር ነቀርሳ መከላከልና መግታት ካልተቻለ አሉታዊ ውጤቱ ከባድ ነው፡፡ ስለሆነም ቁጥጥሩን ማጠንከር፣ የአሰራር ሥርዓቱን ክፍተቶች በመለየት መሙላት ይገባል፡፡ በህገ ወጥ ድርጊቱ የተሰማሩ አካላትን በመለየት ለህግ ማቅረብና መጠየቅ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ በኩል የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉሙሩክ ባለስልጣን ትልቁን ኃላፊነት ይወስዳል፡፡
ባለሥልጣኑ በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስድስት ወራት ሪፖርቱን ሲያቀርብ ኮንትሮባንድ ትልቅ ፈተና እንደጋረጠበት አስታውቋል፡፡ በገቢ አሰባሰብ ሂደቱ ላይም ራስ ምታት እንደሆነበት ነው ያስረዳው፡፡ የምክር ቤቱ አባላትም ኮንትሮባንድን ለማስቆም በኮንትሮባንዲስቶቹ ላይ ጠንካራ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በዚህ በኩል ባለሥልጣኑ ገፍቶ መሄድ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ በህገ ወጥ ድርጊቱ ላይ የተሰማሩ ኮንትሮባንዲስቶች ማንነት እንደሚታወቅም ተመልክቷል፡፡
ይህ ከሆነ ደግሞ እርምጃ የመውሰዱን ሂደት ያቀለዋል፡፡ ቁርጠኝነት ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡ የምክር ቤት አባላትም ክንዳቸውን አፈርጥመው የአገርን ኢኮኖሚ እያዳከመና ህገ ወጥነት እንዲንሰራፍ በር እየከፈተ ያለውን ኮንትሮባንድ ለመከላከልና ለማቆም በተዋናዮቹ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የድርሻቸውን ማበርከት አለባቸው፡፡ እርምጃው ሳይወሰድ ሲቀርም ለምን ብለው መጠየቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የህዝብ እንደራሴ እንደመሆናቸው የህዝብና የአገር ሀብት ዘራፊዎች በህግ እንዲጠየቁ መስራት አለባቸው፡፡
ባለሥልጣኑም ቁርጠኝነትን ተላብሶ በግብር ሥርዓቱ ላይ የተደቀነውን አደጋ ለማስቆም መረባረብ ይኖርበታል፡፡ የወጡ ደንቦችና ህጎች በቅጡ ተፈጻሚ እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ለውጤት መትጋት አለበት፡፡ የኮንትሮባንድ ሰደድ አገርና ህዝብን እጅግ ለከፋ ጉዳት ሳይዳርግ በመከላከሉ ረገድ ህዝቡም የበኩሉን ሚና መጫወት ይጠበቅበታል፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።