Items filtered by date: Thursday, 08 February 2018

 

አዲስ አበባ (ኢዜአ)፡- ሰሜን ኮርያ የኦሎምፒክ ቡድኗን ወደ ውድድሩ ቦታ ለሚያጓጉዘው መርከቧ ተጨማሪ የነዳጅ ድጋፍ መጠየቋን የደቡብ ኮርያው የውህደት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
መርከቧ 210 የቡድኑ አባላትን አሳፍራ ትናንት ከሰዓት በደቡብ ኮርያዋ ሙክሆ ወደብ ከደረሰች በኋላ ጥያቄው መቅረቡን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ባይክ ታኢ ሃዩን ተናግረዋል፡፡
የልዑክ ቡድኑ አባላት በደቡብ ኮርያ ቆይታቸው መርከቧን በማረፊያነት ይገለገሉባ ታልም ነው የተባለው፡፡
ልዑኩ የጠየቀው የነዳጅ መጠንና ጥያቄው የተባበሩት መንግሥታት ባለፈው ዓመት ወደ ሰሜን ኮርያ የሚገባውን የተጣራ ፔትሮሊየም መጠን ለመወሰን ካሳለፈው ውሳኔ ጋር መጣረስ አለመጣረሱ ይፋ አልተደረገም፡፡
ቃል አቀባዩ ጥያቄው እየተጤነ መሆኑን ገልጸው ድጋፉ ከዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ጋር በመመካከር ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታው ቀዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ያስተላለፈው ውሳኔም ሆነ አሜሪካ ከመርከብ ጋር በተያያዘ የጣለችው ማዕቀብ እንደማይጣስም አረጋግ ጠዋል፡፡ ደቡብ ኮርያ የሰሜን ኮርያ መርከቦች በሀገሯ ባህርና ወደቦች እንዳይንቀሳቀሱ የጣለችውን ክልከላ በጊዜያዊነት አንስታለች፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ባለፈው ዓመት ሰሜን ኮርያ ላይ የጣለው ማዕቀብ ወደ ሀገሪቱ የሚላከውን የተጣራ ነዳጅ ምርት በ89 ከመቶ ቀንሶታል፡፡ ማዕቀቡ የኢንዱስትሪ እቃዎችን ጨምሮ ሌሎች ማሽኖች፣ የማጓጓዣ ተሸከርካ ሪዎችና ብረታብረቶች ወደ ሰሜን ኮርያ እንዳይ ላኩ ይከለክላል፡፡ የሰሜን ኮርያን የነዳጅ ጥያቄ በጥርጣሬ አይን የሚመለከቱት ሰዎች መኖራቸ ውንም ሲኤን ኤን በዘገባው አመላክቷል፡፡
ቀደም ብሎ አራት ባለስልጣናትን ጨምሮ 280 ሰሜን ኮርያውያን በየብስ ተጓጉዘው ደቡብ ኮርያ ገብተዋል፡፡ የሰሜን ኮርያውን የኦሎምፒክ ልዑክ የሚመሩት የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔርና የፓርላማው ሃላፊው ኪም ዮንግ ናም የሀገሪቱን መሪ ኪም ጆንግ ኡንን ታናሽ እህት ኪም ዮንና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናትን አስከትለው የፊታችን አርብ ወደ ውድድሩ ቦታ ያቀናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Published in ስፖርት

በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጠባቂ ከሆኑት የስፖርት ፍልሚያዎች መካከል በየአራት ዓመቱ የሚደገሰው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ይጠቀሳል፡፡ በቀጣዩ ሰኔ ወር በሩሲያ አዘጋጅነት የሚካሄደው 18ኛው ዓለም ዋንጫም ከወዲሁ ታዳሚ አገሮችን ለይቶ ለመጀመሪው ቀን ቁልቁል መቁጠር ጀምሯል፡፡ ይሄ የዓለም ዋንጫ በሚጠበቅበት በአሁኑ ሰዓት ከወደ ለንደን አንድ ዜና ተሰምቷል፡፡ ልክ እንደ እግር ኳሱ ሁሉ በአትሌቲክሱም የመጀመሪያውን የዓለም ዋንጫ ለማካሄድ ዝግጅት ተጀምሯል፡፡
ቢቢሲ ትናንት እንደዘገበው፤ የአትሌቲክስ ዓለም ዋንጫ ውድድሩ የሚካሄደው በቀጣዩ ሐምሌ ሰባትና ስምንት ለሁለት ቀናት ነው፡፡ በታላቋ ብሪታኒያ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን በተዘጋጀው የመጀመሪያው አትሌቲክስ ዓለም ዋንጫ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጃማይካ፣ ደቡብ አፍሪካና ፖላንድ የሚካፈሉበት ይሆናል፡፡
አዘጋጇ ብሪታኒያ ከውድድር ማሰናዳት ኃላፊነት ውጪ በማትካፈልበት በዚህ ዓለም ዋንጫ በአትሌቲክሱ ስፖርት ገናና ስም ያላቸው ኢትዮጵያና ኬኒያ አይሳተፉም፡፡ አዘጋጆቹ ለዚህ ያስቀመጡት ምንም ምክንያት የለም፡፡ በውድድሩ አንድ ሴት እና አንድ ወንድ አትሌት ለየውድድር አይነቱ ከየአገራቱ የሚመረጥ ሲሆን፤ እስከ 1500 ሜትር ርቀት ያሉ ውድድሮችን የሚያካሂዱ ይሆናል፡፡
ለሁለት ምሽቶች ብቻ የሚካሄደው ይሄ ውድድር ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት እንደሚያስገኝ ይጠበቃል፡፡ ለዚሁ የሚሆንም በአጠቃላይ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ተዘጋጅቷል፡፡ አዘጋጆቹ እንዳስታወቁት ሽልማቱ የሚገኘው ከተመልካቾች ትኬት ይሆናል፡፡ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ፕሬዚዳንት ሰባስቲያን ኮ፤ ውድድሩ በስፖርቱ ፈጠራ ከታዩ ኹነቶች ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸው ለአዘጋጆቹ የብሪታኒያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና ለለንደን ከተማ ከንቲባ ያላቸውን ምስጋናና አድናቆት ገልጸዋል፡፡
ከስምንት አገሮች ስምንት ቡድኖች የሚኖሩበት ውድድሩ፤ የዓለማችንን ታዋቂና ድንቅ አትሌቶች የሚያካትት እንደሚሆን የጠቆሙት ሰባስቲያን ኮ፤ ለስፖርቱ ተመልካቾች ከሚፈጥረው የውድድር አማራጭ ባሻገር እያንዳንዱ አትሌትም ውድድሩን ለማሸነፍና ሽልማት ለማግኘት የሚፎካከርበት ይሆናል፡፡
የብሪታኒያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሊቀመንበር ሪቻርድ ቦውከር በበኩላቸው፤ ለመጀመሪ ጊዜ የሚሰናዳው ውድድር ተመራጭ ዝግጅት እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የሁለት ቀኑ ውድድር ያለዙር ውድድርና ያለማጣሪያ በቀጥታ ለፍፃሜ የሚደረግ ፍልሚያ ነው›› ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ይሄም የውድድሩ አስደሳች ጎን ያደርገዋል፡፡
የመጀመሪያው አትሌቲክስ አለም ዋንጫ በሚካሄድበት ሳምንት ሁለት ከፍተኛ ትኩረት የሚስቡ ውድድሮች ፍፃሜያቸውን ያገኛሉ፡፡ አንደኛው በሩሲያ አዘጋጅነት የሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ በዚያው በእንግሊዝ አገር የሚካሄደው የዌምበልደን የሜዳ ቴኒስ ውድድር ፍፃሜ ያገኛል፡፡ የስፖርቱን ዓለም ተመልካች ቀልብ የሚስቡት እነዚህ ሁለት ውድድሮች በተለያዩ መድረኮች በሚካሄዱበት ቀናት ስለምን አዲስ የውድድር ፎርማት መፍጠር አስፈለገ? የሚለው በራሱ መልስ የሚሻ ጥያቄ እንደሚሆን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡
የመርሃግብር አወጣጡን አስመልክታ በማሕበራዊ ድረገፅ ትችቷን ያሰፈረችው የብሪታኒያዋ አትሌት ኬሊይ ሶተርተን አዲሱ መርሃግብር ከተጠባቂዎቹ ፍልሚያዎች ጋር መገጣጠሙ ለተመልካቹ መልካም አጋጣሚ አለመሆኑን አስታውቃለች፡፡ የአትሌቷን ትችት የተከላከሉት የብሪታኒያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሊቀመንበር ሪቻርድ ቦውከር ግን፤ ውድድሩ ሲዘጋጅ የመርሃግብሩ መገጣጠም የታሰበበት መሆኑን ጠቅሰው የአትሌቲክስ ውድድሩ የሚካሄድበት ኦሎምፒክ ስቴዲየም የፕሪምየር ሊጉ ክለብ ዌስትሃም ዩናይትድ የሚጠቀምበት በመሆኑ በዓለም ዋንጫ ምክንያት ውድድር ስለማያስተናግድ በማሰብ መሆኑን አስታው ቀዋል፡፡
የለንደን ከተማ ከንቲባ ሳዲቅ ካን፤ በውድድሩ ወቅት ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡትን ምርጥ አትሌቶችንና የስፖርቱ አፍቃሪዎች ለመቀበል ታላቋ ከተማችን ዝግጁ ናት ሲሉ አስታውቀዋል። አዲስ በሚጀመረው የአትሌቲክሱ ዓለም ውድድር ብዙ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ይገኛሉ፡፡ ከአትሌቲክሱ ዓለም ያሉ ባለሙያዎች አዲሱ ውድድርን በመልካም ጎኑ ሲመለከቱ የመርሃግብር አወጣጡ ከተወዳጁ እግር ኳስ ዓለም ዋንጫ ጋር መግጠሙ አጋጣሚነት ያልተዋጠ ላቸውም ብዙዎች ናቸው፡፡ የሆነው ሆኖ ‹‹ፀሐይ አይጠልቅባትም›› የምትባለው የእንግሊዟ መዲና ለንደን በፊፋ የተነፈገችውን የእግር ኳሱ ዓለም ዋንጫ ፍልሚያ አዘጋጅነት ዕድል በአትሌቲክሱ በማግኘቷም የተፅናናች ይመስላል፡፡

ብሩክ በርሄ

Published in ስፖርት

ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የተሳተፉበት የዓለም የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድር ትላንት በጀርመን ዱሲልዶርፍ ከተማ ሲካሄድ፤ በአንጻራዊነት ኬንያዊያን አትሌቶችን ባለ ድል አድርጓ አልፏል፡፡
በትናንቱ ውድድር በወንዶች የ60፣ 800፣ የ1 ሺህ 500 እና የ3 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድሮች እንዲሁም የ60 ሜትር መሰናከልን ጨምሮ የአሎሎ ውርወራና የምርኩዝ ዝላይ የተካሄደ ሲሆን፤ በሴቶች ደግሞ በ60፣ 400፣ 800 እና 1 ሺህ 500 ሜትር ከተደረጉ ውድድሮች በተጨማሪ የ60 ሜትር መሰናከል እንዲሁም የርዝመት ዝላይ ውድድር ተካሂዷል፡፡
ውድድሩ የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬ ሽኖች ማህበር በተያዘው ዓመት ከሚያካሂዳቸው ስድስት የቤት ውስጥ ውድድሮች ሁለተኛው ሲሆን፤ የመጀመሪያው ውድድር ባሳለፍነው ሳምንት በጀርመን ካርልስሩህ ከተማ ተካሂዷል። በትናንቱ ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶችና በ3 ሺህ ሜትር ወንዶች ተሳትፎ አድረገዋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት በጀርመን ካርልስሩህ ከተማ በተካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በ1ሺህ 500 ሜትር ሩጫ ሶስት ደቂቃ ከ57 ሴኮንድ ከ45 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት ማሸነፏ የሚታወስ ነው። አትሌት ገንዘቤ የገባችበት ሰአት በርቀቱ የቤት ውስጥ ውድድር ሁለተኛው ፈጣን ሰአት ሆኗል። በዚህኛው ዱሲልዶርፍ ውድድር ላይ ደግሞ ኬንያውያዊቷ ዊልሰን ጂቤትና ፖላንዳዊቷ አንጀሊካ ቺቾካ ከኢትዮጵያኖቹ አትሌቶች ጋር ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ቢገመትም ርቀቱን ኬኒያዊቷ ባትሪስ ችብኮች በኬንያ ታሪክ የቤት ውስጥ ውድድር ክብረወሰን በመስበር ጭምር በአሸናፊነት አጠናቅቃለች፡፡ በዚህ ውድድር አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬና አትሌት ዳዊት ስዩም የማሸነፍ ቅድሚያ ግምት ቢሰጣቸውም ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡
በወንዶች የ3 ሺህ ሜትር ውድድር አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻና አትሌት ደጀን ገብረመስቀል ተሳትፈዋል፡፡ አትሌት ዮሚፍ በሳምንቱ ውድድር በጀርመን ካርልስሩህ ከተማ በተካሄደው የዓለም ቤት ውስጥ ውድድር በ3ሺህ ሜትር ተወዳድሮ በአገሩ ዜጋ ሐጎስ ገብረህይወት ተቀድሞ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል። ትናንት በተደረገው ውድድር በዚሁ ርቀት ስፔናዊው አዴል ሜቻልና ኬንያዊው ዴቪስ ኪፕላጋት ከኢትዮጵያውያኖቹ አትሌቶች ጋር ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ግምት የተሰጠ ሲሆን፤ ርቀቱን ዮሚፍ ቀጄልቻ ሰባት ደቂቃ፤ከአርባ ሰከንድ፤ሀምሳ አምስት ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ማሸነፍ ሲችል፤ ኬኒያዊው ብትዌል በርጂን ሁለተኛ ወጥቷል፡፡ ሌላው ስፔናዊ አትሌት አዴል ሜቻል በሶስተኝነት አጠናቋል፡፡
በ1ሺህ 500ሜትር የወንዶች ውድድር ኬንያዊው ቪንሰንት ኪቤት በቀዳሚነት ሲያጠናቅቅ፤ ኢትዮጵያዊው አማን ዎጤ ሁለተኛ ሲወጣ፤ ሌላው ኬንያዊ ኤሊጃህ ማናንጓይ ርቀቱን በሶስተኝነት ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ 800ሜትር ኬኒያውያን አትሌቶች ከአንድ እስከ ሁለት ተከታትለው ሲገቡ ፖላንዳዊው አደም በሶስተኝነት ጨርሷል፡፡
በትናንቱ የዱሲልዶርፍ ውድድር በ60ሜትር ቻይናዊው ቢንግቲያን ሱ የእስያውያንን ክብረወሰን በመስበር አሸናፊ መሆን ችሏል፡፡
ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በቀጣዮቹ 20 ቀናት በስፔን ማድሪድ፣ በአሜሪካ ቦስተን፣ በፖላንድ ቶሩን እና በስኮትላንድ ግላስኮው ከተሞች የተቀሩትን አራት ዓለም አቀፍ የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድሮችንም ያካሂዳሉ።

አዲሱ ገረመው

Published in ስፖርት
Thursday, 08 February 2018 17:32

ሁለተኛ ዲግሪዬን ልይዝ ነው

‹‹ሁለተኛ ዲግሪዬን እየተማርኩ ነው›› ብላችሁ ምን ትላላችሁ? ቆይ እስኪ ልገምት፡፡ አንዳንዱ ‹‹ብርቅ ነው እንዴ ታዲያ!›› የሚል ይመስለኛል፡፡ ግዴላችሁም ብርቅ ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ በጣም የሚያስፈራኝ ጥያቄ ‹‹በመጀ መሪያው ዲግሪ ምን ሰራህበትና !›› የሚል ካለ ነው፡፡ ኧረ ተው ጎበዝ! ይሄ የምጽፈው ነገር ለመጀመሪያ ዲግሪ አነሰ እንዴ? እንዲያው የሰራሁት አኩሪ ሥራ ባጣ ነው እንጂ ከአራተኛ ክፍል ተነስተው ድንቅ የፈጠራ ሥራ የሰሩ እንዳሉ እኮ ተስቶኝ አይደለም፡፡ እኔማ ዲግሪዬን ያህል ነገር ይዤ የእነርሱን ፈጠራ እንኳን በአግባቡ መቼ አወኩና!
ለማንኛውም ሁለተኛ ዲግሪዬን ልይዝ ነው፡፡ ‹‹እንዴት›› ማለት ጥሩ ነው፡፡ አሁን እየተማርኩት ያለው የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቴ ያለምንም ክፍያ፣ ምንም ተጨማሪ ጊዜ ሳያስፈልገኝ (ለትምህርት ጊዜ ሳላባክን አይባልም ብዬ ነው)፣ ምንም መምህር ሳያስፈልገኝ ነው፡፡ አሁንም ‹‹እንዴት›› ማለት ጥሩ ነው፡፡ ቆይ ግን ከዚያ በፊት ምንድነው የምማረው የሚለው ይቅደም፡፡
በነገራችን ላይ አብዛኛው ሰው የሚማረው ትምህርት ግን ምን ይመስላችኋል? እኔ ግን የምጠይቃቸው ሰዎች አብዛኞቹ ‹‹አካውንቲንግ›› ነው የሚሉኝ (ደግሞ በጥናት የተረጋገጠ እንዳይመስልህ)፡፡ እኔ ደግሞ ከቁጥር ጋር የተያያዘ ትምህርት እንዴት እንደሚያስፈራኝ፡፡ ቆይ ግን አካውንቲንግ የተማረ ሁሉ ሀብታም ይሆናል እንዴ? ከሆነ እኔም እሞክረዋለሁ ብዬ ነው፡፡ ለነገሩ ሀብታም ባይሆኑም ዝም ብሎ ብር መደመር፣ መቀነስ፣ ማባዛት፣ ማካፈሉ ደስ ሳይል አይቀርም፡፡
ወደ እኔ ሁለተኛ ዲግሪ ስንመጣ ይህን ትምህርት የመረጥኩት ራሴ አይደለሁም፡፡ አሉ አይደል አንዳንድ ተማሪዎች 12ኛ ክፍል ጨርሰው ፎርም ሲሞሉ ‹‹የትኛውን የትምህርት መስክ ልምረጥ?›› እያሉ የሚጨነቁ? እንዲህ ዓይነት ተማሪዎች ሰው የመረጠላቸውን ነው የሚማሩት፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ግን በኩረጃ ያለፉ መሆን አለበት፡፡ እና እኔም በኩረጃ ነው ያለፍኩት ማለት ነው? እስኪ ተወኝ ወዳጄ!
ሁለተኛ ዲግሪዬን እየተማርኩ ያለሁት በግዴታ ነው (ይገርማል እኮ)፡፡ ደግሞ እኮ ግዴታውም በጓደኛ ወይም በቤተሰብ ቢሆን ጥሩ ነበር፡፡ በጎረቤቴ ግዴታ ነው እየተማርኩ ያለሁት፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡
ጎረቤቴ ማኔጅመንት እየተማረ ነው፡፡ ያው እንግዲህ ታውቃላችሁ አይደል አንዳንድ ሰዎች ሲያነቡ ድምጽ እያሰሙ ካልሆነ አይገባቸውም መሰለኝ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ነው፡፡ እናም ይሄ ልጅ ሁሌም ማታ ማታ (ቀንማ የት ያገኘኛል) ድምጹን ከፍ አድርጎ ነው የሚያነበው፡፡ በተለይ ‹‹ፕሬዜንቴሽን›› ያለበት ቀን ደግሞ እንዲሁ እንደተወነ ነው የሚያድር፡፡ ከእኔ ቤት የመጣ ሰው ከጎን ያለው ሲኒማ ቤት እንጂ መኖሪያ ቤት ላይመስለው ይችላል፡፡
ኧረ ልጁማ አንዳንዴም ያስቀኛል፡፡ ጥያቄና መልስ ውድድር ራሱ የሚያዘጋጅ ይመስለኛል፡፡ ራሱ ይጠይቃል ራሱ ይመልሳል፡፡ ‹‹ኖ! ኖ! ኖ! መልሱ ልክ አይደለም›› እያለ ደግሞ ይሟገታል፡፡ ይሄ ልጅማ ‹‹ጠሽ›› ነገር ሳይሆን አይቀርም፡፡ ቆይ መልሱ ልክ ካልሆነ ለምን እንደዚያ ብሎ ይመልሳል? ልክ ነው ብሎ ከሆነስ የመለሰው ልክ አለመሆኑን ማን ነገረው? እንግዲህ ሰው ስህተቱን ራሱም ያገኘው ይሆናል፡፡
ከትወናው ወጣ ባለ ቀን እንግዲህ ድምጹን ከፍ አድርጎ ‹‹ሀንድ አውቱን›› ያንበለብለዋል፡፡ የሚገርመኝ ነገር ማንበብ በጀመረ ቁጥር የሚጀምረው Defnition of Manegement ከሚለው ነው፡፡ ልጁማ ጎበዝ ተማሪ መሆን አለበት፡፡ አንድ ተማሪ መጀመሪያ የሚማረውን የትምህርት ዓይነት ትርጉም ነው ማወቅ ያለበት፡፡ ጽንሰ ሃሳቡ ምን እንደሆነ እስከሚገባው ድረስ መቀጠል አለበት፡፡ ልጁ Manegement is… ብሎ የጀመረ እንደሆነ ከነትርጓሜው፣ ታሪካዊ ዳራውን፣ የአገራትን ተሞክሮ ሁሉ ያነበንባል፡፡ እኔ ብቻ ዝም ብዬ ማድመጥ ነው፡፡ በዚህ አያያዜ እኔ የምበልጠው ሁሉ ይመስለኛል፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ራሱን ጥያቄ ይጠይቅና መልሱ ሲጠፋበት ጠርቼ ልነግረው ሁሉ ይቃጣኛል፡፡ እንደምሰማው ካወቀ ክፍያውን አግዘኝ ይለኛል ብዬ ነው የምተወው፡፡
እኔ እምለው? አንዳንድ ሰዎች ግን ለምንድነው ምሥጢር የሆነውን ነገር ሁሉ የሚዘከዝኩት? እስኪ በመንገድ ላይ በታክሲ ውስጥ ልብ ብላችሁ ታውቃላችሁ? ታክሲ ውስጥማ እኮ የማይሰማ አስገራሚ ነገር የለም፡፡ አንዳንዱ የቤቱን ገመና ሁሉ ጮክ እያለ ነው የሚያወራ፡፡ እርግጥ ነው አንዳንድ አስቸኳይ ጉዳይ ሊኖር ይችላል፡፡ አንዳንዶቹ ግን መቼውንም ቢወራ ችግር የሌለውን ነገር ታክሲ ውስጥ ሆነው ማዝራት ነው፡፡
ሌላው ምሥጢር የማይደብቅበት ቦታ እንግዲህ አዲስ አበባ ውስጥ ተከራይተህ ስትኖር ነው፡፡ በቤትህ ውስጥ የምትከታተለው አንተ የፈለከውን ጣቢያ ሳይሆን የጎረቤትህን ምርጫ ነው፡፡ ዜና መስማት ፈልገህ እንኳን ቢሆን ጎረቤትህ ሙዚቃ ከሆነ ያማረው በግድህ ትሰማታለህ፡፡ አንተ በሬዲዮ ወይም በቴሌቪዥን የእንግዳ ፕሮግራም መከታተል ፈልገህ ቢሆን ጎረቤትህ ዜና ከፈለገ በግድህ ትሰማታለህ፡፡ በጣም የሚያናድዱኝ ደግሞ ድምጹን ለምን እስከ ላንቃው እንደሚለቁት ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች እኮ የማይሰሙትን ከፍተውት ሁሉ ይሄዳሉ፡፡
እንግዲህ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራም በግድም ቢሆን መከታተሉ ባልከፋ ነበር፡፡ ዳሩ ግን የሚያወሩትን ወሬም ለመከታተል ትገደዳለህ፡፡ አንተ የማታወራውንም ለማስማት ትገደዳለህ፡፡ እንቅልፍ መተኛት የሚቻለው ጎረቤቶችህ ከተኙ ብቻ ነው፡፡
ለማንኛውም እኔ የማኔጅመንት ትምህርቴን እየተማርኩ ነው፡፡ ትምህርቱ ደግሞ የንድፈ ሃሳብ ብቻ አይደለም፡፡ የተግባር ልምምድም ጭምር ነው፡፡ ጎረቤቴ የንድፈ ሃሳቡን ትምህርት ይሰጠኛል፤ አከራዬ የተግባር ልምምዱን ይሰጡኛል፡፡ ለነገሩ አከራዬማ እኮ የማኔጅመንት ትምህርት ብቻ አይደለም የሚሰጡኝ፡፡ የፍልስፍና ትምህርት ይሰጡኛል፣ የሥነ ልቦና ትምህርት ይሰጡኛል፣ የሒሳብ ትምህርት ሰጥተውኛል፡፡ ሁሉንም ትምህርት በተግባር ልምምድ ነው የሚሰጡኝ፡፡
ለመሆኑ የጀመርኩት የማኔጅመንት ትምህርት መቼ ይጠናቀቅ ይሆን? ስለምርቃት የሚያወራበትን ቀን እየጠበቅኩ ነው፡፡

ዋለልኝ አየለ

 

Published in መዝናኛ

ወጣት ተማሪዎች በሚማሩባቸው በሁለተኛ ደረጃ እና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች ከኢትዮ ጵያውያን ወግ፣ ባህልና አኗኗር ያፈነገጡ በዓላት እየተበራከቱ ከመጡ ሰነባብተዋል፡፡ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች እነዚህ በዓላት በስፋት ሲከበሩ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ በዓላቱ ተማሪዎችን ከማህበረሰቡ ባህልና ወግ እንዲያፈነግጡ ከማድረግም ባሻገር የተማሪዎችን ቤተሰቦች ለአላስፈላጊ ወጪ እየዳረገ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ በዓላቱ ለተማሪዎቹ እውቀትና ክህሎት ዕድገት ምንም ፋይዳ የሌላቸው መሆናቸው ይነሳል፡፡ የነገ ሀገር ተረካቢ ወጣቶች በእንዲህ መልኩ ለባዕድ በዓላት አከባበር ትኩረት መስጠታቸው ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በ2006 ዓ.ም ያካሄደው ዳሰሳዊ ጥናት እነዚህ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እየሆኑ መምጣታቸውን ያመላክታል፡፡ የእነዚህን በዓላት አከባበር ፈር ለማስያዝ ቢሮው ከከተማው ባህልና ቱሪዝም ቢሮና ከፍትህ ቢሮ ጋር በመሆን በ2007ዓ.ም መመሪያ አውጥቷል፡፡ መመሪያውን የግልና የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ እንዲያደርጉት ወርዶላቸዋል፡፡
በቢሮው የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዑመር ኢማም እንደሚሉት፤ በመዲናዋ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚከበሩ አንዳንድ በዓላት ተማሪዎችን ከማህበረሰቡ ባህል፣ ወግ፣ ልማድና ሃይማኖት ውጪ ሊያደርጉ የሚችሉ ከመሆናቸውም ባሻገር ተማሪዎችም ጉዳት እስኪደርስባቸው የሚያደርጉ ክስተቶች ይስተዋል ባቸዋል፡፡ ተማሪዎች ወደ ፊት ብሄራዊ አንድነትን፣ የሀገር ፍቅር ለማዳበር ምንም ፋይዳ የሌላቸው በዓላትን እንደሚያከብሩ በተደረገው ጥናት ተለይቷል፡፡
የተዘበራረቁትን የበዓላት አከባበር ጉዳይ ፈር ማስያዝ በማስፈለጉ የትምህርት ተቋማት የበዓላት አከባበር እና የትምህርታዊ ጉብኝት የሚል መመሪያ ወጥቷል፡፡ በመመሪያው ለተማሪዎች እውቀትና ክህሎት ዕድገት እንዲሁም ለኢትዮጵያውያን ወግ፣ ባህልና ልምድ ዕድገት አስተዋጽኦ የሌላቸው ክሬዝ ዴይ፣ ፉል ዴይ ወዘተ የመሳሰሉ በዓላት እንዳይከበሩ መደንገጉን ገልጸዋል፡፡
አቶ ዑመር እንደሚሉት፤ እነዚህ ለተማሪዎች እና ለሀገር ጥቅም የሌላቸው በዓላት በመመሪያው መሰረት ሙሉ በሙሉ ተከልክለዋል፡፡ በአንጻሩ የሀገር ፍቅርን፣ ክብርን እና አንድነትን ሊያጠናክሩ የሚችሉ የሰንደቅ ዓላማ፣ የብሄር ብሄረሰቦች፣ የዓድዋ ድል በዓላትን የመሳሰሉ በዓላት እንዴት መከበር እንዳለባቸውም መመሪያው ላይ ተካቷል፡፡
መመሪያው ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ከግል ትምህርት ቤት ባለሃብቶችና የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን ከሚመሩ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ በወይይቱም ባለድርሻ አካላቱ አስተያየት ሰጥተውበት በመመሪያው አስፈላጊነትም ላይ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ መመሪያው በሚተገበርበት ወቅት ደግሞ መመሪያውን የሚፈጽሙ አካላት በየደረጃው እንዲያውቁና ስለአፈጻጸሙ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል፡፡ በዚያው መሰረት የተለያዩ ክፍለ ከተሞች ስልጠና ተሰጥቷቸው ተግባራዊ እያደረጉት ነው፡፡ መመሪያውን ተግባራዊ በማያደርጉት ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎች ተቀምጠዋል፡፡
አቶ ዑመር እንደሚሉት፤ መመሪያው ወጣ ማለት ግን እነዚህን በዓላትን በድብቅ የሚያከብሩ ተማሪዎች ሊኖሩ አይችሉም ማለት አይደለም፡፡ በመሆኑም የበዓላት አከባበር ዙሪያ ፈቃድ የሚሰጡ ኮሚቴዎች በትምህርት ቤቶች ተዋቅረዋል፡፡ ተማሪዎች የተለያዩ በዓላትን ከማክበራቸው በፊት በትምህርት ቤቶች ላሉ ኮሚቴዎች ማቅረብ አለባቸው፡፡ ኮሚቴውም በዓሉ ከመመሪያው ጋር የሚጣረስ ሆኖ ከተገኘ እንዳይከበር ውሳኔ ያስተላልፋል፡፡ በኮሚቴው ያልተፈቀደ በዓል የሚያከብሩ ተማሪዎች ካሉ በተማሪዎች የዲስፕሊን መመሪያ ላይ በተቀመጠው መሰረት ከማስጠንቀቂያ ቀላል ቅጣት ጀምሮ እስከ ከባድ አንድ ዓመት ድረስ ማባረር ቅጣት ተቀምጧል፡፡
መመሪያው ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገ ቢሆንም በተለያዩ ክፍለ ከተሞች እና ትምህርት ቤቶች ወጥ የሆነ አተገባበር የለም፡፡ አንዳንድ ክፍለ ከተሞች በመመሪያው ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት ገና አሁንም ስልጠና በመስጠት ላይ ናቸው፡፡ በዚያው ልክ ቀድመው ስልጠና ሰጥተው መተግበር የጀመሩ ክፍለ ከተሞችና ትምህርት ቤቶችም አሉ፡፡ ሁሉም ትምህርት ቤቶች መመሪያውን በአፋጣኝ መተግበር እንዲጀምሩ ቢሮው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እንደሚሰራም አቶ ዑመር አረጋግጠዋል፡፡
የካቲት 12 መሰናዶ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ደምረው አሰፋ እንደሚሉት፤ ትምህርት ቤቱ ቀደም ባሉ ጊዜያትም ተማሪዎች እንዲያከበሩ ይፈቅድ የነበረው ውስን በዓላትን ብቻ ነበር፡፡ እነዚህም የሰንደቅ ዓላማ ቀን፣ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን እንዲሁም ሌሎች መንግሥት በካላንደር የሚዘጋቸውን በዓላትን ተማሪዎች እንዲያከብሩት ያደርጋል፡፡ ከዚያ ውጪ ግን ከውጭ ሀገራት የመጡ የምዕራባውያን በዓላትን ለማክበር አንዳንድ ተማሪዎች ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ትምህርት ቤቱ ግን እውቅና አልሰጣቸውም፡፡ ይልቁኑ እነኝህ በዓላት የኢትዮጵያውያን እንዳልሆኑና በዓላቱ እንዲከበሩ የሚያስገድዱ ምንም ምክንያቶች እንደሌሉ ለተማሪዎቹ አበክሮ የማስረዳት ሥራ እየሰራ ነበር፡፡
እነዚህ በዓላት ለተማሪዎቹ ምንም ዓይነት ፋይዳ የሌላቸው ስለመሆኑ በሰንደቅ ዓላማ መስቀልና ማውረድ ወቅት ሚኒሚዲያዎችን በመጠቀም ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ አንዳንድ ተማሪዎች ግን የትምህርት ቤቱን መመሪያ በመጣስ በግልጽም በድብቅም ከማክበር ወደ ኋላ አላሉም፡፡ ‹‹ዋተር ዴይ›› በማለት ውሃ የመራጨት፤ ‹‹ክሬዚይ ዴይ›› በማለት ደግሞ የተበጫጨቁ ልብሶችን ለብሰው የመምጣት ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ እስከ 2008 ዓ.ም ይህ አከባበር በመጠኑ ይታይ የነበረ ሲሆን ከዚያ ወዲህ እንደዚህ ዓይነት በዓላት አከባበሮች ማስቀረት ተችሏል፡፡ ለዚህም ቢሮው ያወጠው መመሪያ መውጣት እና አመራሩ እነዚህ በዓላት እንዳይከበሩ በወሰደው ቁርጠኛ እርምጃ እገዛ ማድረጉን ይጠቅሳሉ፡፡
አቶ ደምረው እንደሚናገሩት፤ ቢሮው ያወጠው መመሪያ ትምህርት ቤታቸው ቀደም ብሎ በማንነቱ የሚኮራና ሀገሩን የሚወድ ዜጋ ለማፍራት ያደርግ የነበረውን ጥረት ከማገዙም ባሻገር የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑ ወጣቶች በሀገራቸው ባህል እንዲኮሩ የሚያደርግ ነው፡፡ መመሪያው የዘገየ ቢሆንም መውጣቱን በበጎ ጎኑ ይመለከቱታል፡፡ ግን መመሪያው በመመሪያነቱ በራሱ የሚፈለገውን ለውጥ አያመጣም፡፡ መመሪያው ለውጥ ማምጣት የሚችለው ተቋማት በዚህ ዙሪያ በትኩረት ሲሰሩ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ከሚመለከታቸው ጋር የመተማመን ሥራ ተሰርቶ ህዝቡ አውቆ እንዲተገብረው የማድረግ ሥራዎች መሰራት አለባቸው፡፡
ትምህርት ቤቱ መመሪያውን ለመምህራን በስልጠና መልክ ሰጥቷል የሚሉት አቶ ደምረው፤ ለተማሪዎች በአንድ ቀን ጉባዔ ስለ መመሪያው ግንዛቤ ለማስጨበጥ አዳጋች በመሆኑ በየወቅቱ ሰንደቅ ዓላማ ከመውጣቱ እና ከመውረዱ በፊት የአሥር ደቂቃ መልዕክት ይተላለፋል፡፡ በዚያ ወቅት የዚህ መመሪያ ጉዳይ እየተላለፈ ነው፡፡ በመመሪያው ዙሪያ ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጎን ለጎንም የእርምት እርምጃዎች እየተወሰዱ ናቸው፡፡ ይህን ነገር አድርገው የሚገኙ ተማሪዎችን ወላጅ በማስመጣት ውይይት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ አቶ ደምረው ማብራሪያ፤ ትምህርት ቢሮ መመሪያ አውርዶ ዝም ማለት የለበትም፡፡ መመሪያው እየተተገበረ መሆን አለመሆኑን የራሱ የሆነ ክትትል ድጋፍ እና ጥናቶችን በማካሄድ አተገባበሩ ያለበትን ደረጃ መገምገም አለበት፡፡ መመሪያው በወጥነት እየተተገበረ መሆኑንም መከታተል አለበት፡፡ በወጥነት እየተተገበረ ካልሆነም ምክንያቱም ለይቶ የሚተገበርበትን ሁኔታ ማፈላለግ አለበት፡፡
በየካቲት 12 መሰናዶ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው በሱፈቃድ ቦንሴ እንደሚናገረው፤ እሱ በሚማርበት ትምህርት ቤትም ሆነ የእሱ ጓደኞች በሚማሩባቸው የመዲናዋ ትምህርት ቤቶች እነዚህ ከምዕራባውያን የተኮረጁና ለኢትዮጵያውያን አስፈላጊ ያልሆኑ በዓላት ሲከበሩ ተመልክቷል፡፡ እንዲያውም ሰሞኑን ዋተር ዴይ በመባል የሚታወቅ በዓልን የተወሰኑ ተማሪዎች ውሃ በመራጨት ሲያከብሩ እንደነበር በራሳቸው ትምህርት ቤት መመልከቱን ያነሳል፡፡
በዓሉን የሚያከብሩ ተማሪዎች ቁጥር ጥቂት ቢሆንም አብዛኞቹ ተማሪዎች እነዚህን በዓላት የማክበር ፍላጎት እንደሌላቸውም ያነሳል፡፡ «እነዚህ በዓላት ለኢትዮጵያውያን ምናቸውም አይደሉም፡፡ ምንም ትርጉምም የላቸውም፡፡ ስለዚህ አስፈላጊ አይደሉም» ይላል፡፡ ይልቁኑ እነዚህን በዓላት ተማሪዎች እንዳያከብሩት ትምህርት ቤቶች እና ቢሮው መመሪያ በማውጣት ብቻ ዝም ብለው የሚመለከቱት ከሆነ የኢትዮጵያውያን በዓላት ላይ የራሳቸው የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያስከትሉ ይችላሉ ባይም ነው፡፡ ስለዚህ መመሪያ አውጥቶ ብቻ ከመተው ይልቅ መመሪያውን ተግባራዊ በማድረግ ለማስቆም ርብርብ መደረግ አለበት፡፡
እንደ ተማሪ በሱፍቃድ ማብራሪያ፤ አንዳንዶቹ የምዕራባውያን በዓላት በትምህርት ቤቶች በሚከበሩበት ወቅት የሀገር ባህልና ወግ ላይ የራሳቸው የሆነ አሻራ እያሳረፉ ከመሆናቸውም ባሻገር የሀገሪቱ ውስን ሀብት እንዲባክንም እያደረጉ ናቸው፡፡ በቅርቡ በትምህርት ቤታቸው በውስን ተማሪዎች ‹‹ወተር ዴይ›› ተማሪዎች ውሃ በመረጫጨት ሲያከብሩ እንደነበር ያነሳል፡፡ በዚህ በዓል ምክንያት በርካታ ዜጎች ንጽህ የመጠጥ ውሃ አጥተው በሚቸገሩበት ኢትዮጵያ ውሃ መባከኑ ተገቢነት የለውም፡፡
የራዲካል አካዳሚ ርዕሰ መምህር አቶ ሀጎስ ኃይሉ እንደሚሉት፤ ትምህርት ቤታቸው የችግሩን አሳሳቢት ቀድሞ በመረዳት የምዕራባዊ ዓለም መነሻ ያላቸው በዓላት በትምህርት ቤቱ እንዳይከበሩ ከ2003 ጀምሮ አግዶ ነበር፡፡ የኢትዮጵያውያን ወግና ባህል የሚያንጸባርቁ ውስን በዓላት ብቻ በትምህርት ቤቱ ይከበሩ ነበር፡፡ ሆኖም በ2007 ዓ.ም በትምህርት ቢሮ የወጣው መመሪያም ከአንድ ወር በፊት ለትምህርት ቤቱ ደርሷል፡፡ መመሪያው ለትምህርት ቤታቸው ሳይደርስ ዓመታት መቆጠራቸው ተገቢነት የለውም፡፡
«መመሪያው የሚታየውን የባህል ወረራ ለመከላከልም የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አለው» የሚሉት አቶ ሃጎስ ትምህርት ቤታቸው ከሰባት ዓመት ወዲህ ለመተግበር ይሞክር የነበረውን አሰራር የሚያግዝ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ሆኖም መመሪያው በሁሉም ትምህርት ቤቶች በወጥነት እየተተገበረ አለመሆኑን ጠቅሰው በወጥነት እንዲተገበር ቢሮው የጀመረውን ጥረት ማጠናከር እንዳለበት ነው ያመለከቱት፡፡

 

መላኩ ኤሮሴ

Published in ማህበራዊ

የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ማዕከላዊ ኮሚቴ የተጀመረው የለውጥ ጉዞና የወደፊት አቅጣጫ ለ10 ቀናት ዝርዝር ግምገማ በማድረግ ትናንት ማምሻውን በስኬት አጠናቋል።
ግንባራችን ኢህአዴግም በጥልቅ ለመታደስ የጀመረውን ንቅናቄ ዳር ለማድረስ በቅርቡ ራሱን ገምግሞ አቅጣጫ ማስቀመጡ የሚታወስ ሲሆን ከግምገማው በመነሳትም ሀገራችን ኢትዮጵያና ክልላችን በፖለቲካዊ፤ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስኮች ያለችበትን ሁኔታ በዝርዝር በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጧል።
አስር ቀናት በፈጀው የአሁኑ ውይይታችን፣ የሕዝባችን ሰላምና አብሮነት በምንም መልኩ አደጋ ውስጥ እንዳይገባ የክልላችን ሕዝቦች እና መሪ ድርጅቱ ኦህዴድ በቅንጅት በመስራት የሀገራችንን ሕልውና መታደግና የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ በስኬት እንዲጠናቀቅ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶ ተወያይቷል። ድርጅታችን ከሚታወቅባቸው መለያ ባህሪያቱ እያንዳንዱ ጉድለቶቹን ያለማመንታት መቀበልና ለማረም ጥረት ማድረግ መሆኑ ይታወቃል። ይህ የዴሞክራሲያዊ ድርጅት ባህሪ በመሆኑ ከሕዝብ የሚነሱ ቅሬታዎችን ማድመጥ፣ ሕዝቡን ከልብ ይቅርታ የመጠየቅና የእርምት እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን በዝርዝር በመምከር አቅጣጫ አስቀምጧል።
የፌዴራል ሥርዓቱን አደጋ ውስጥ ሊጥሉ የሚችሉ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶችን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ለይቶ አፋጣኝ እርምጃዎችን በመውሰድ የሕዝቡን መሻት ማሳካት ለነገ የማይባል ጉዳይ መሆኑን በዝርዝር ተመልክቷል፡፡ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ አሳታፊ የፖለቲካ ስርዓት፣ ሰላምና ፍትህ እንዲሰፍን በጥብቅ ዲስፕሊን በመስራት የሕዝብ እርካታን ማረጋገጥ ጊዜ የማይሰጠው መሰረታዊ አጀንዳ ስለመሆኑ መክሯል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በመተባበር የሀገራችንን ቀጣይ ጉዞ የማቅናት ሚናውን ዛሬም እንደትናንቱ መጫወት እንደሚገባውም ተወያ ይቷል፡፡
በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ያለውን ግንኙነት በዴሞክራሲ አግባብ በማጠናከር የጋራ አላማችንን ለማሳካት ርብርብ ማድረግና የሀገሪቱን ሕልውና ከአደጋ መከላከል እንደሚገባ በዝርዝር በመምከር አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
የፌዴራላዊ ሥርዓታችንን አደጋ ላይ የጣሉ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን፣ ሕዝቡ በመሪ ድርጅቱ ላይ እንዲያምጽ ያስቻሉ የመልካም አስተዳደር እጦቶችን፤ስልጣን ህዝብን ማገልገያ መሳሪያ መሆኑን በመዘንጋት በርስትነት ይዞ ለግል ምቾትና ጥቅም ቅድሚያ መስጠትን፣ በነጻነት ተዘዋውሮ የመስራት መብትን ነፍጎ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሕዝቦችን እስከማፈናቀል የደረሰ ድርጊትን፤ በኢንቨስትመንት ስም የመንግሥትና የህዝብ መሬት መመዝበሩን፤ እንዲሁም የሕዝቦች ሰላምና ፀጥታ መደፍረሱን እና የመሳሰሉትን እየተፈጸሙ ያሉ አደገኛ ድርጊቶችን ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ አምርሮ በመታገል የሀገራችንን ሕልውና መታደግ ልዩ ትኩረት የሚሹ አበይት ጉዳዮች መሆናቸውን በዝርዝር ተመክሮባቸ ዋል፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተከሰቱ ግጭቶች የበርካታ ዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፤ የሕዝቦች በሰላም ውሎ ማዳር፣ ወጥቶ መግባት ከፍተኛ ስጋት ላይ ወድቋል፡፡ ለእነዚህ ችግሮች መከሰት ኃላፊነቱን ወስዶ እርማት ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ አጽንኦት ሰጥቶ በመምከር አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
የፌዴራል ሥርዓቱን አደጋ ላይ በመጣል ግላዊና ቡድናዊ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ በንጹሃን ዜጎች ሕይወት ላይ አደጋ ያደረሱና በታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ ፀያፍ ድርጊቶችን የፈጸሙ ኃይሎች በሕግ እንዲጠየቁ ለማድረግ፣ እንዲሁም መሰል ስህተት እንዳይደገምና የሕግ የበላይነት በመላ ሀገሪቱ እንዲሰፍን ለማስቻል ሕዝቦችን በማሳተፍ ትግሉን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር የግድ መሆኑን ከግንዛቤ አስገብቶ ማዕከላዊ ኮሚቴው አቅጣጫ አስቀምጧል።
ቀንደኛ የሕልውናችን ጠላት ድህነት መሆኑ ቢታወቅም ይህንን ጠላት ለመዋጋት በመንግሥት፣ ድርጅትና ሕዝብ ትስስር ሊሰራ እንደሚገባውና አዳዲስ ሃሳቦችን እያፈለቀ አመራር የመስጠት ጉዳይ ከድርጅታችን እንደሚጠበቅ ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
ሀብት ማመንጨት ብቻ ሳይሆን ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ማስቻል፣የሀብት አጠቃቀምንም ከብክነት የጸዳ ማድረግ፣ ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ አሰራር በማስፈን ሕዝቡ እንዲያለማ ከማስቻል በዘለለ የመቆጣጠር ሚናውንም ከፍ ማድረግ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
አዳጊ ኢኮኖሚን የሚያንኮታኩቱ መጥፎ ልማዶችን በተለይም ሙስና፣ ኮንትሮባንድ፣ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ፍላጎቱን ማኮላሸት፣ የአቅርቦት ሰንሰለቱን ማስተጓጎል፣ ማንኛውም የገበያ ፍትሃዊነትን የሚያዛቡ አሉታዊ ተግባራትን አጥፍቶ በምትኩ በዘመናዊነት የታገዘ ፍትሃዊ አሰራርን መዘርጋት፣ ያልተገባ የጥቅም ትስስር ያላቸውን ሰንሰለቶች በጥናት ላይ በመመስረት የመበጣጠስ ተግባር በተቀናጀና የሪፎረም ሥራውን በሚያሳልጥ መልኩ እንደሚፈፀም አቅጣጫ ተቀምጠዋል፡፡
ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌዎች ሳይሸራረፉ ተግባር ላይ እንዲውሉ፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ዜጎች ካለምንም ስጋት ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው እንዲሰሩ በማስቻል በፍትህ ሥርዓቱና በፖሊሲ ሥርዓታችን ላይ ተጨባጭ ለውጥ ሊያስገኙ የሚችሉ ሁለንተናዊ ሪፎርም ማከናወን እንደሚገባ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
ከክልሎች ጋር የጀመርነውን ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ህግ መንግሥታዊነቱን ጠብቆ እንዲቀጥልና ፌዴራላዊ ሥርዓታችን ይበልጥ መጠናከር የሚችልበት ሁኔታ አጽንኦት ተሰጥቶት ተመክሮበታል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ የመቻቻል ፤የመደጋገፍና አብሮ መኖር እሴቶችን ያዳበረ በመሆኑ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በመከባበርና በፍቅር አብሮ በመኖር የሁሉም ዜጎች መብት በእኩል እንዲከበር ከወንድም ሕዝቦች ጋር አብሮ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ጥላቻን በጥላቻ፣ክፉ ተግባርን በሌላ ያልተገባ ድርጊት መመከት ሊቆም ይገባዋል፡፡ በመሆኑም ተከሰቱ ለሚባሉ ችግሮች ሁሉ መፍትሄው ፍትሃዊና ሕጋዊ የትግል ስልትን መከተል መሆኑ ታምኖበት ከጥፋት ተግባራት በመታቀብ ኦሮሙማን በሚያጎላ አቃፊ መሆን እንደሚገባ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሕዝቦች ጋር የነበረንን መልካም ግንኙነት በመመለስ እንደ ወንድማማች ሕዝቦች የባይተዋርነት ስሜት እንዳይፈጠር በሚያስችል መልኩ በታላቅ የኃላፊነት ስሜት እንዲመራ ጊዜያዊ ችግሮችን ፈተን ለዘላቂ የጋራ ጥቅሞቻችን በወንድማማችነት መንፈስ እንድንረባ ረብ የሶማሌም ይሁን ሌሎች ብህረ ብሄረሰቦች በኦሮሞ ባህልና የገዳ ሥርዓት ባስተማረን መልኩ በፍቅርና በአብሮነት እንዲኖሩ ለማስቻል ሕዝቡ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ማዕከላዊ ኮሚቴው ጥሪ አቅርቧል፡፡
የሃሳብ ልዩነቶችን ማጥፋት አስቸጋሪ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ስለሆነም ሁል ጊዜ ለውይይትና ለክርክር አውድ ማስፋት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበ ታል፡፡ ፍላጎትን በውይይት እንጂ በኃይል የማስረጽ ዝንባሌ እንዳይታይ በቀጣይነት መስራት እንደሚያስፈልግም መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
ዛሬ አድገው የሀገራቸውን ህዝብ ኑሮ በከፍተኛ ደረጃ ያሻሻሉ ሀገራት ታሪክ ሲመረመር በአገራዊ ጉዟቸው ውስጥ ሕዝባዊ አመጽን ያስተናገዱ፣ የወጣቶች ቁጣ የደረሰባቸውና መሰል አጋጣሚዎችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ መቀልበስ የቻሉት የዘላቂ ልማት ባለቤት እንደሆኑ ታሪካቸው ያሳያል፡፡ በመሆኑም በወጣቶች ላይ የሚታየውን ፍትህ የመሻት ቁጣ ሀገርን በማያፈርስ መልኩ ከኃይል በፀዳ ሁኔታ ሰላማዊ የትግል ስልት እንዲከተሉ በማስተማር የዴሞክራሲ ባህልን ማዳበር አስፈላጊ መሆኑን ኮሚቴው ያምናል፡፡ ዋነኛ ሚናውም የተሻለች ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ማሸጋገር በመሆኑ የተሻለች ሀገር ብቻ ሳይሆን ብቁ ተረካቢ ወጣቶችን ማፍራት እንደሆነም ይገነዘባል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ እየታየ ያለው ድርቅ፣ ግጭት፣ስደት፣ የሕዝብ መብዛትያልተደራጀ ኢኮኖሚና ያልዳበረ የዴሞክራሲ ባህል ባለበት ሀገር ነገሮች እንዲባባሱ ከማድረግ አልፎ የሀገር ህልውናን አደጋ ውስጥ እስከመጣል እንደሚደርስ ታውቆ የተሻለች ሀገር የመፍጠሩና ብዙ ተረካቢ የማፍራቱ ተግባር በጥንቃቄና በኃላፊነት ስሜት እንዲከወን በዝርዝር ተመክሯል፡፡
ይህንንም ከማሳካት አኳያ ቅድሚያ ከተሰጣቸው ተግባራት መካከል ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ወገኖችን ከጊዜያዊ መጠለያ ወደ ቋሚ ቦታ ማስፈር፤ የወጣቶችን የሥራ አጥነትን በመቀነስ የኑሮ ሁኔታቸውን ማሻሻል፤ የመልካም አስተዳደርና ብልሹ አሰራሮችን ማስተካከል፤ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን ማዘመን፤ፍርድ ቤት፣ አቃቤ ህግ፣ ፖሊስ፣ የወረዳና የቀበሌ መዋቅሮችን መልሶ ማደራጀት፤ ሰላምና ፀጥታ በማስከበር የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይገኙ በታል፡፡
በመላ የሀገራችን ህዝቦች ይሁንታ አፋን ኦሮሞ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ድርጅታችን ይሰራል፡፡ በተጨማሪም በሂደት ላይ ያሉና ያልተጠናቀቁ መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄዎች በጥብቅ ዲስፕሊን እንዲፈጸሙ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡
በድርጅቱ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ፤መድረኩ የሚጠይቀውን የትግል ልክ በብቃት ለመፈፀም፣ በቀጣይም ጥንካሬውን አጎልብቶ መጓዝ ይችል ዘንድ 14 የኢህአዴግ ምክር ቤት አባላት እንዲተኩ እና 4 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትም እስከሚ ቀጥለው ጉባዔ እንዲታገዱና አንድ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በማስጠንቀቂያ እንዲታለፍ የወሰነ ሲሆን፣ የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ የማስፋትና የአመራሩን የሃሳብና የተግባር አንድነት ይበልጥ ማጠናከር በቀጣይነት እንዲሰራበት ተመክሯል፡፡
ለኦሮሞ ሕዝብ
ለዘመናት ትከሻህ ላይ ተጭኖ የነበረውን የጭቆና ቀንበር ለመስበር ሁልጊዜም ታሪክ እየዘከረው የሚኖር አኩሪ መስዋዕትነት ከፍለሃል፡፡ በከፈልከው መስዋዕትነት ከሌሎች ወንድሞችህ ጋር በመሆን አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር፤ እኩልነት፣ ፍትህ፣ ዴሞክራሲና ሁሉን አቀፍ መብቶች የተረጋገጡባትን የበለፀገች ሀገር ለመገንባት መሰረት ጥለሃል፡፡ በተጀመረው የግንባታ ሂደት ውስጥ የመጡ ተስፋ ሰጪ ድሎች እንዳሉ ሁሉ የጭቆና መሰረት የሆኑ አስተሳሰቦችና አሰራሮችን የሚፈጥሩ አዝማሚያዎ ችም ይታያሉ፡፡ በእነዚህ አዝማሚያዎች ላይም የጀመርከውን ትግል አጠናክረህ መቀጠል ያንተም ሆነ የወንድም ሕዝቦች የሕልውና ጉዳይ ነው፡፡
የመደብ ጭቆና ምን ያህል አስከፊ እንደሆና አዎንታዊ ለውጥን እንደሚገታ ባለፈው ታሪክህ ካንተ በላይ የሚገነዘብ የለም፡፡ በአሁኑም ሰዓት ተመሳሳይ መደባዊ ጭቆና ዳግም በሀገራችን እንዳያቆጠቁጥ ትግልህን አጠንክረህ መቀጠል ይገባሃል፡፡
በሁሉም የታሪክ ምዕራፎች ኢፍትሃዊነትና ጭቆናን ባለመቀበል ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመሆን መስዋዕትነት እየከፈልክ ወደ ድል ስትራመድ እንደነበረው ሁሉ አሁንም ሀገራችንን የገጠሟትን ፈተናዎች በታጠቅከው የገዳ ስርዓት ቱባ ባሕል መሰረት ብሄር፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን በማቀፍና ከጎንህ በማሰለፍ ትግሉን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ህልውና በማስጠበቅ ለውጧን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ የማስቀጠል ኃላፊነትህን እንድትወጣ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ለኦሮሚያ ክልል ወጣቶች
የክልላችንም ሆነ ሀገራዊ ለውጦች ያለወጣቱ ተሳትፎና መሪነት የሚታሰብ አይደለም፡፡ በዚሁ መሰረት እስካሁን በሀገራችን የመጡ ለውጦች በወጣቱ ተሳትፎና አኩሪ መስዋዕትነት የመጡ መሆናቸውን ኦህዴድ ይገነዘበዋል፡፡ ወጣቶቻችን በሁሉም መስክ የተጀመሩ የለውጥ እንቅስቃሴና መልካም ጅምሮች ወደ ላቀ ድል እንዲሸጋገሩ በባለቤትነት መሳተፍና ኃላፊነትን መወጣት፣ ይህንንም በተደራጀ መልኩ መተግበር ይገባዋል፡፡ ወጣቱ በሁሉም መስክ የሚያደርገውን ትግል ምክንያታዊና ሳይንሳዊ በሆኑ ሃሳቦች እየተመራ፤ ዴሞክራሲያዊነትን በጠበቀና ተደማሪ ለውጦችን በተንከባከበ መልኩ የሁሉም መብት ተከብሮ፣ የሀገራችንም ህልውናና የክልላችን ሰላም እንደተጠበቀ የሚቀጥልበት አካሄድ እንዲረጋገጥ ግንባር ቀደም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ድርጅታችን ኦህዴድ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ለኦሮሞ ምሁራን
በሁሉም የታሪክ ምዕራፍ ላይ የኦሮሞ ሕዝብ ባለፈበት የትግል ሂደት ውስጥ እናንተም መስዋዕትነት ከፍላችኋል፡፡ አሁንም በደረስንበት የትግል ምዕራፍ ውስጥ ከሕዝባችሁና ከመሪው ድርጅታችሁ ኦህዴድ ጋር በመሰለፍ ዋንኛው ሥራ የሆነውን ሃሳብን የማፍለቅና የትግሉን አቅጣጫ በጥናትና በምርምር የማሳየት የማይተካ ሚናችሁን እንደሁል ጊዜው መወጣት ይኖርባችኋል፡፡ ድርጅታችን ኦህዴድ፣ ምሁራንን ባላቸው አደረጃጀትም ሆነ በግል ክህሎታቸው፣ እውቀትና የአመራር ብቃትም ጭምር አብሮ ለመስራት የጀመረውን ሥራ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ አጠናክሮ ለመቀጠል ወስኗል፡፡ በዚሁ መሰረት የተከበራችሁ የኦሮሞ ምሁራን የጀመራችሁትን ጠንካራና ተኪ የሌለው ሚናችሁን በመወጣት አጠናክራችሁ ትግሉን እንድትቀጥሉ፣ ለስኬትም እንድትረባረቡ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ለኦሮሚያ ክልል መንግሥት ሠራተኞች
የኦሮሞ ሕዝብ ባደረገው ትግል የራሱን ክልል መስርቶ ያሉበትን ችግሮች ለመፍታትና ራዕዮቹን ለማሳካት ትልቅ የመንግሥት መዋቅር ዘርግቷል፡፡ በዚህ መዋቅር ውስጥ የሕዝባችንን ችግር መፍታት የሚቻለው ከእውቀትና ክህሎት በተጨማሪ ጠንካራ ዲስፕሊን ባለው የመንግሥት ሠራተኛ ነው፡፡ በመሆኑም፣በመንግሥት መዋቅር ውስጥ እየፈጠረበት ያለውን የመብት ጥሰት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ እየተስፋፋ ያለው ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ኢ-ፍትሃዊነትና የዴሞክራሲ እጦት ችግሮችን ለመፍታት የክልላችን መንግሥት ሠራተኞች ቁልፍ ሚና አላችሁ፡፡ሕዝባችንን አንገት ያስደፋውን ዋነኛ ችግሩን በመቅረፍ ብልጽግናን ለማስፈን፣ የማስፈፀም አቅምን ለማጎልበት፣ቀን ከሌሊት ተግታችሁ የመስራት ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ለኦሮሚያ ክልል የፀጥታ አካላት
በክልላችን ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ከሕዝባችን ጋር በተለይም ከወጣቶች ጋር በመቀናጀት የሕዝባችንን ጥቅምና ሀብት ሲዘርፉ የነበሩ ኮንትሮባንዲስቶች ላይ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም በክልላችን የተጀመረውን ሪፎረም ለማደናቀፍ ዝርፊያ ድርጊታቸውን ማስቀጠል የሚፈልጉ የተደራጁ ኪራይ ሰብሳቢዎች የከፈቱትን ጥቃት ለመመከት በግንባር ቀደምነት ተሰልፋችሁ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍላችኋል፡፡ በዚሁም የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ሕልውና እንዲቀጥል ድርሻችሁን በመወጣት ከአደጋ እየታደጋችሁ ትገኛላችሁ፡፡
የኪራይ ሰብሳቢዎች ቡድን በመንግሥት ስልጣን የመክበር አባዜ ከስር ተነቅሎ፣ የሕግ የበላይነት ሰፍኖ እስኪሸነፍ ድረስ የጀመራችሁትን ትግል ሕዝብን በማሳተፍ በከፍተኛ ዲስፕሊን ሕዝባዊ ኃላፊነታችሁን መወጣት ይገባችኋል፡፡ በክልላችን አስተማማኝ ሰላምና የሕግ የበላይነት የተረጋገጠበት፣ እንዲሁም ፍትህ የሰፈነበት እንዲሆንና ዜጎቻችን መብታቸው ተከብሮ ሥርዓት አልበኝነት እንዳይኖር የተሰጣችሁን ተቋማዊ ኃላፊነት ከሕዝብ ጋር በመቆም ሕዝባዊ በሆነ መንፈስ እንድትወጡ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ለኦህዴድ አባላት
ተንሰራፍቶ የቆየውን ጭቆና ለማስወገድ ሕዝባችን ሲያካሂድ የነበረውን መራራ ትግል ውስጥ የመርነት ሚናን ተቀብለህ መስዋዕትነት በመክፈል የዛሬው ምዕራፍ ላይ እንዲደርስ የበኩልህን አስተዋፅኦ አበርክተሃል፡፡ ጠንካራ ድርጅት ያለ ጠንካራ አባል ሊታሰብ አይችልም፡፡ ኦህዴድ ያለበትን ታሪካዊ ኃላፊነት እንዲወጣ አሁን በደረሰበት የትግል መድረክ የሚመጥን ቁመና እንዲኖረው ለማስቻልና ለማስቀጠል የድርጅታችን አባላት የድርጅታችሁን አላማ በጥብቅ ዲስፕሊን ለማሳካት ቀን ከሌሊት መታገል ይገባችኋል፡፡ ሕዝባችን በተለያየ ደረጃ እያደረገ ባለው ትግል ውስጥ አባሎቻችን በግንባር ቀደምነት በመሳተፍና በመምራት ችግሮችን በኃላፊነት መፍታት ይገባቸዋል፡፡ አሁን የደረስንበት የትግል ምዕራፍ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት በቅድሚያ በመክፈል ለሌሎች ምሳሌ በመሆን የድርጅታችሁን ተልዕኮ በተሰማራችሁበት መስክ ሁሉ በማሳካት የሕዝባችንን ጥያቄ በአፋጣኝ እየመለሰ፣ ትግሉን በግንባር ቀደምነት በመምራት አዲሲቷን ኢትዮጵያ እውን የማድረግ ኃላፊነቱን የሚወጣ፣ ጠንካራና ከለውጥ ጋር ራሱን የሚያሳድግ ድርጅት እውን እያደረጉ መጓዝ ትኩረት የሚሻ በመሆኑ ይህንንም በብቃት መወጣት ይገባችኋል፡፡
በውጭ ሀገራት ለሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች
በኦሮሞ ሕዝብ የለውጥ ጉዞ ውስጥ ባላችሁ እውቀትና ሀብት በተደራጀም ሆነ ባልተደራጀ መልኩ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ ለመወጣት ስታደርጉ የነበረውን ርብርብ የሚፈታተኑ ሁኔታዎች እንደነበሩ እና መድረኮችም አስቸጋሪ እንደነበሩ ኦህዴድ ይገነዘባል፡፡ በሕዝባችን አንድነትና ሁለንተናዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ በእውቀት፣ በቴክኖሎጂ፣ባላችሁ ተሞክሮዎችና ትስስር፣ በሀብትና በመሳሰሉት ሁሉ እንድትሳተፉና የሕዝባችንን ችግር በጋራ እንድንፈታ፤ የሚያስፈልጉ ሁኔታዎችም እንዲመቻቹ ኦህዴድ ጠንክሮ እንደሚሰራ ሊያረጋግጥ ይወዳል፡፡ በዚሁ መሰረት በውጭ ሀገር የምትኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች በሕዝባችን ጥቅም ላይ ያለምንም ድንበርና ልዩነት በጋራ እንድንሰራ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ለኢህአዴግ አባል ድርጅቶች
ድርጅታችን ኢህአዴግ፣በሀገራችን ሕዝቦች ላይ የተጫነውን ፀረ-ዴሞክራሲ፣ ድህነት፣ የመልካም አስተዳደር እጦትና ኋላቀርነትን ለመፍታት ባደረገው እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ድሎችን ማስመዘገብ የጀመረው በውስጡ ያለውን ችግር በተከታታይ በመፈተሽና በመፍታት ላይ ነው፡፡ በቅርቡ በኢህአዴግ ደረጃ በተደረገ ግምገማ በእህት ድርጅቶቹ መካከል የተፈጠረው ያልተገባ ግንኙነት በሂደትም ወደ ጥቅም ቡድንተኝነት እያደገ በመምጣቱ የነበረውን ግንኙነት እያሻከረ እንዲሄድ አድርገዋል፡፡ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴም ጉዳዩን በጥልቀት በመገምገም ማንኛውም ግንኙነቶች መርህና መርህ ላይ ብቻ እንዲመሰረቱና ዴሞክራ ሲያዊ ትግልን ማዕከል ያደረጉ እንዲሆኑ ለማስቻል ትኩረት ሰጥቶ ተወያይቶበት አቅጣጫ አስቀም ጧል፡፡ በዚሁ መሰረት የእህት ድርጅቶች አሁን በደረስንበት የትግል ምዕራፍ በግንባራችን ኢህአዴግ ተገምግመው አቅጣጫ የተቀመጠባቸውን ጉዳዮች ያለምንም መሸራረፍ እንዲፈፀሙና የሕዝባችንን ጥያቄ ለመመለስ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት ርብርብ እንድናደርግ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ለተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች
በብዝሃነት ለተገነባች ሀገራችን ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ መሆኑ እሙን ነው፡፡ እንደ ነብር ዥንጉርጉር የሆነው የእርስ በርስ ግንኙነታችን የሃሳብ ልዩነትን ማስተናገድ የሚያስችል አሰራርና ባህል ማዳበር ያስፈልገዋል፡፡ ከኃይል የፀዳ፣ በውይይትና በምክክር የሚያምን፣ ይበልጥ ለሀገር የሚበጅ ሃሳብ የሚፈልቅበት የውይይት ባህል እንዲዳብር የፖለቲካ ድርጅቶች ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህ ወሳኝ ወቅት የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች አስተዋይነትና አርቆ አሳብነት የሚፈተ ንበት ጊዜ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በመቀራ ረብና በመነጋገር የፖለቲካ ባህላችንን እንድናሻሽል ብሎም የሀገራችንን መፃኢ ዕድል በጋራ ማበጀት እንችል ዘንድ ተቀራርበን እንድንሰራ ድርጅታችን ይፈልጋል።
ዴሞክራሲ ለሀገራችን ሕዝቦች የሕልውና ጉዳይ ነው። ዴሞክራሲ ለመገንባት የሃሳብ ልዩነቶች የሚስተናገዱበት ማዕቀፍና አሰራር እንዲሁም ባህልና አስተሳሰብ እንዲዳብር የፖለቲካ ፓርቲዎች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ኦህዴድ በሚገባ ይገነዘባል፡፡ የሀገራችን ሕዝቦች አማራጭ ሀሳቦች እየቀረቡለት በዴሞክራሲያዊ ሂደት የሚጠቅመውን ሃሳብ እንዲመርጥ፣ለፖለቲካ ፓርቲዎች በሕገመንግሥቱ የተቀመጡ ቃልኪዳኖች ያለመሸራረፍ እንዲተገበሩና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ኦህዴድ ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፖርቲዎች ጋር በቅርበት እንደሚሰራ በጥልቅ ተወያይቶበት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ በዚሁ መሰረት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያላችሁ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ በሀገራችንና በሕዝባችን የጋራ ጥቅም ላይ ከድርጅታችን ኦህዴድ ጋር አብራችሁን እንድትሰሩ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ለኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች
የኢትዮጵያ ብሔር፤ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በችግርም ሆነ በመልካም ጊዜ በጋራ ተፈትነው ትናንትን መሻገር ችለዋል። ለገጠማቸው ፈተናዎችም እኩል የታገሉና መስዋትነት የከፈሉ ህዝቦች ናቸው። ሀገራችን ህልው ሆና እንድትቀጥል ከማስቻላቸው ባሻገር በዓለም ታሪክ ውስጥ ጉልህ ቀለም እንዲኖራት አድርገው ለዛሬ ትውልድ አስረክበዋል። በአባቶቻችን ተጋድሎ የተገነባችውን ኢትዮጵያ እኛም አስውበንና አንድነቷን አስጠብቀን ለቀጣይ ትውልድ የማሻገር ታሪካዊ ኃላፊነት አለብን። በአንድ እጅ ማጨብጨብ አይቻልምና ይህን ኃላፊነታችን በብቃት እንድንወጣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር፣ የጋራ እሴቶቻችንን በማጎልበት፣ የተጀመረው መልካም ጅማሮ ዳር እንዲደርስ እጅ ለእጅ ተያይዘን ለስኬቱ በጋራ እንድንረባረብ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያስተላልፋል።
የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ የ10 ቀናት የለውጥ ግምገማ ቆይታ ድርጅቱ ለአገራችን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ጉዞ ስኬት እንዲሁም ለህዝቦች እኩል ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ በላቀ ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት ለማከናወን ዝግጁነቱን ያረጋገጠበት መድረክ እንደሆነ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አረጋግጧል።

Published in ፖለቲካ

የአየር ንብረት ለውጥ እና መዘዞቹ ኢትዮጵያ በርቀት ሆና የምትመለከተው ሳይሆን በየጊዜው እየተከተለ የሚፈታተናት ተግዳሮት ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ በዚህ ችግር ምክንያት በተለያዩ ጊዜያት በሚከሰት ድርቅ ዜጎቿ ለአደጋ ይጋለጣሉ፡፡ ድርቅ በሚያስከትለው ረሃብ ዜጎቿ ውድ የሆነውን ህይወታቸውን ማጣታቸውም የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ለዚህ ችግር ሀገሪቷና ዜጎቿ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እምብዛም ባይሆንም የችግሩ ገፈት ቀማሽ ከመሆን ግን አላመለጡም፡፡ የችግሩ ምክንያቶች ምን ይሁን የት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለመቋቋም ግን ጥረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ሁሉንም ያግባባል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወንም የአንድ ተቋም ተግባር ሳይሆን የሁሉንም ቅንጅታዊ አሰራር የሚጠይቅ ነው፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ ተቋም ይህን በመገንዘብ በሚያከናውኑት ተግባራት ውስጥ እንደተጨማሪ ሥራ ሳይሆን ዋነኛው ተግባራቸው አድርገው ሊመለከቱት ይገባል፡፡ ይህን ችግር ለመቋቋም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት በተለያዩ ዘርፎች ግቦች ተጥለዋል፡፡
በአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር የአየር ንብረት ለውጥ እቅድ ዝግጅት ሜይን ስትሪሚንግ ዳይሬክተር አቶ አብይ ኃይለ ገብርኤል እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን የትኩረት አቅጣጫ አድርጋ እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡ የተጀመረው የኢኮኖሚ ዕድገት በአየር ንብረት ለውጥ ፍጥነቱ እንዳይገታ ማድረግ፣ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀው ጋዝ መጠን መቀነስ እንዲሁም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ማህበረሰብ መገንባት ዋነኛው ዓላማው ነው፡፡
ለዚህም የፌዴራል ተቋማትና ክልሎች ዋና ፈጻሚ ተደርገው የሚታሰብ ሲሆን፤ የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር አቅጣጫ የመስጠት፤ አፈጻጸም የመገምገም እንዲሁም የተለያዩ መመሪያዎችን የማውጣት ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ሚኒስቴሩ የማስፈጸም ሥራ የመስራት ኃላፊነት የተጣለበት ሲሆን፣ የማስፈጸሚያ ሰነዶችን ማዘጋጀት፣ ተቋማት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ እንዲያካትቱ አድርጓል፡፡ በአምስት ዓመቱ እቅዳቸው ውስጥ ያካተቱትን ደግሞ በየዓመቱ እቅድ ውስጥ እየሸነሸኑ እንዲያካትቱ የማድረግ ሥራ እንዲሁም አስፈላ ጊውን የቴክኒክ ድጋፍ የመስጠትና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን መስራት ዋነኛው ተግባሩ ነው፡፡
እንደ እርሳቸው ገለፃም፤ ሚኒስቴሩ ከ15 የፌዴራል ተቋማት ጋር በቅንጅት ይሰራል፡፡ ሁሉም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች አረንጓዴ ኢኮኖሚ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አደረጃጀት መፍጠር አለባቸው፡፡ በእቅዳቸው ውስጥ ያካተቱትን ለመተግበር የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው በመፈጸም አፈጻጸማቸውን በየደረጃው ለሚመለከት አካል ያቀርባሉ፡፡
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሁሉም አካል ያለው ግንዛቤ እየተሻሻለ መምጣቱ፣ የተወሰኑ ተቋማት ይህ ተግባራት አደረጃጀት ዘርግተው መስራት መጀመራቸው፤ መስሪያ ቤቶች ይህንን አፈጻጸም የሚገመግም ኮሚቴ በማቋቋም እየገመ ገሙ ተግባሩ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ የመለየት ሥራ እየተከናወኑ መሆናቸው በጎ ጅምር ነው፡፡ ተቋማቱ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዙ በርካታ ፕሮጀክቶችን መተግበር መጀመራቸው የሚበረታታ ነው፡፡
ሚኒስቴሩ በየጊዜው በሚያደርገው ግምገማና የመስክ ምልከታ ተግባራቱን በመፈጸም ረገድ የተቋማቱ አፈፃፀም ጉራማይሌ መሆኑን ለመታዘብ መቻሉን ይጠቅሳሉ፡፡ «አንዳንድ ተቋማት አደረጃጀት ዘርግተው ለጉዳዩ ትኩረት አድርገው እየሰሩ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ጉዳዩን እንደተጨማሪ ሥራ በመመልከት አደረጃጀት ሳይዘረጉ ይንቀሳ ቀሳሉ» ይላሉ፡፡ አደረጃጀት ዘርግተው የሚንቀሳቀ ሱት የተሻለ አፈጻጸም እያሳዩ ሲሆን፣ ያለአደረጃጀት እንደተጨማሪ ሥራ እየሰሩ ያሉት ደግሞ አፈጻጸማቸው ውስንነት የታየበት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ የአደረጃጀቱ ወጥ ያለመሆን ለአፈጻጸም ጉራማይ ሌነት ምክንያት እንደሆነም ያመለክታሉ፡፡ አደረጃጀት እንዲኖር የማድረግና ያለማድረግ ኃላፊነት የተቋማት ኃላፊዎች ቢሆንም አንዳንድ ኃላፊዎች ለጉዳዩ በሚሰጡት አነስተኛ ግምት አደረጃጀቱን እንዳይዘረጋ እንቅፋት ፈጥሯልም ባይ ናቸው፡፡
እንደ አቶ አብይ ማብራሪያ፤ የፌዴራል ተቋማቱ በክልል ካለው አደረጃጀቶች ጋር ያላቸው ቁርኝት አጥጋቢ አይደለም፡፡ ለክልሎች አስፈላጊውን ድጋፍ ያለማድረግ አዝማሚያዎችም ይስተዋላሉ፡፡ ተቋማት ከዚህ ቀደም በተለመደው አሰራር ሥራቸውን መቀጠላቸውም ሌላኛው ችግር ነው፡፡ ይሁንና በተለመደው አሰራር አየር ንብረት ለውጥን መቋቋም አይቻልም፡፡ በመሆኑም ተቋማት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያከናውኑትን ተግባራት በቴክኖሎጂዎች ማስደገፍ አለባቸው፡፡ እንዲሁም በሁሉም ሥራ የባለሙያ ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡
በቀጣይ የአደረጃጀት ችግሮችን ለመፍታት የጠራ አደረጃጀት ያላቸውንና የሌላቸውን የመለየት ሥራ እንደሚሰራ የሚናገሩት አቶ አቢይ፤ የእውቀት ክፍተት ላለባቸው አቅም የመገንባትና የማስፈጸሚያ ሰነዶች በማቅረብ አፈጻጸማቸው ወጥ እንዲሆን ያግዛል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም መስሪያ ቤቶች ጉዳዩን የሚፈጽም የራሱ የሆነ አደረጃጀት እንዲኖረው ማድረግና የፌዴራል ተቋማቱ ከክልል አደረጃጀቶች ጋር ያላቸውን ቁርኝት እንዲያጠናክሩ ጥረት እንደሚደረግም ነው ያስገነዘቡት፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ቤት ማሻሻል ፕሮግራም ባለሙያ አቶ ሰይፉ ወልዱ እንደሚሉት፤ በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ በቅድመ መደበኛ፣ በመጀመሪያ ፣ በሁለተኛ ደረጃ እና በመሰናዶ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በደረጃቸውና አቅማቸው በተፈጥሮ ሀብት እና እንክብካቤ ላይ ያላቸውን ግንዛቤ እና እውቀት ለማሳደግ በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።
የአካባቢ እንክብካቤ እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን የተመለከቱ ርዕሰ ጉዳዮች በሥርዓተ ትምህርቱ ተካተው እየተሰጠ ከመሆኑም ባሻገር በትምህርት ቤቶች የአካባቢ እንክብካቤ ክበብ፣ አረንጓዴ ክበብ፣ አገርህን እወቅ ወዘተ ክበባትን በማቋቋም ተማሪዎች ስለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ወይም እንክብካቤ ፣ የተፈጥሮ ሀብት ሲጎዳ ስለሚያስከትላቸው ጉዳቶች ፣የተመናመኑ የተፈጥሮ ሀብቶችን መልሶ ለማቋቋም መከናወን ስላለባቸው ጉዳዮች እርስ በርስ እና እውቀቱ ያላቸውን ሰዎች በመጋበዝ ይማማራሉ። የተማማሩትን ትምህርት ወደ ተግባር ለመለወጥ ከሚለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በትምህርት ቤታቸው ቅጥር ግቢ እና በማህበረሰቡ ውስጥ በመገኘት ችግኝ በመትከል እና በመንከባከብ ሥራ እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡
አቶ ሰይፉ እንዳብራሩት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በእረፍት ሰዓት በሚኒ ሚዲያ አማካኝነት ግንዛቤ እንዲያገኙ፣ በአካባቢ እንክብካቤ እና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዙሪያ የተከናወኑ በጎ ተግባራትን በማቅረብ ይህንን ፈለግ እንዲከተሉ ይደረጋል። በአካባቢ እንክብካቤ እና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዙሪያ የተለያዩ የጥያቄ ውድድሮችን በማካሄድ የተማሪዎች እና የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ግንዛቤ እንዲያድግ ይደረጋል። በአካባቢ እንክብካቤ እና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዙሪያ የተሻለ አፈጻጸም ላሳዩ ተማሪዎች በትምህርት ቤቱ አቅም የተለያዩ ማበረታቻዎችን በመስጠት ሌሎች የእነርሱን አርአያ እንዲከተሉ ይደረጋል።
በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የዘርፈ ብዙ ትምህርት ቡድን አስተባባሪ አቶ ደረጃ ደምሴ እንዳሉት 293 የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የአካባቢ ጥበቃ ክበባት አሉ፡፡ እነዚህ ክበባት ይህን ሥራ እየሰሩ ናቸው፡፡ ግማሹ ከጽዳት ጋር፣ ግማሹ ከችግኝ ተከላ፣ ግማሹ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ የሚሰሩ ናቸው፡፡ ይህ ለግል ትምህርት ቤቶችም ወርዷል፡፡
በእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ማስተባበሪያ ዩኒት አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ አሰፋ እንደሚሉት፣ የግብርና ዘርፍ በአየር ንብረት ለውጥ ከሚጎዱ ዘርፎች አንዱ ነው፡፡ ይህን ተጽዕኖ ለመቋቋም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚሰሩ ሥራዎችን የመደበኛ ሥራ አካል አድርጎ ይሰራል፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድም የመደበኛው ሥራ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ምን መደረግ አለበት በሚለው ዙሪያ 41 የሚሆኑ ተግባራት ተለይተዋል የተለዩ ተግባራትም የህብረተሰቡን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በመደበኛ ሥራ ተካቶ እንዲሰራ እየተደረገ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ክልሎች የሚገኙ ቢሮዎችም የእቅዳቸው አካል አድርገው እንዲሰሩ እየተደረገ ነው፡፡
ለእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ላይ የበኩሉን መወጣት አንዱ ዋነኛው ሥራ ነው፡፡ ይህን ተግባር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ከመደበኛ ሥራቸው አንዱ እንዲያደርጉት ከመደረጉ በፊት ጀምሮ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም እገዛ የሚያደርጉ ሥራዎችን ሲሰራ የነበረ ሲሆን በፕሮጀክት ደረጃ በመቅረጽ በሁሉም ክልሎች በሚገኙ 35 ወረዳዎች የተሰሩ ሥራዎች ግብርናን ከአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለማላቀቅ ከሚደረጉ ጥረቶች ጋር ተጣጥሞ እንዲሄድ ለማድረግ ተሰርቷል፡፡
ሥራዎቹም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም አስተዋጽኦ ከማበርከታቸውም በላይ የህብረተሰቡ የገቢ ምንጭ የሚሆኑ፣ ለችግር ተጋላጭነትን የሚቀንሱ፣ ምርትና ምርታማነትን በዘላቂነት ለማሻሻል የሚያስችሉ መሆናቸው እንደታየ ይናገራሉ፡፡ ከዚያ በተጨማሪም በነዚህ ፕሮጀክቶች የአየር ንብረት ለውጥን የሚያባብሱ ከግብርና የሚለቀቁ ሙቀት አማቂ ጋዞችን ለመቀነስ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችንም ተግባራዊ ሲደረጉ ነበር፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ መስሪያ ቤቶች የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ሥራን እንደ ዋነኛ ሥራቸው እንዲመለከቱት መደረጉን ተከትሎ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸውም የበፊቱን ጥረት አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በዚህም አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገቡ ናቸው፡፡ በእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ዘርፍ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚን ለመገንባት ከሚደረገው ጥረት አንዱ የተፈጥሮ ሃብት ልማት፣ ጥበቃ እና ክብካቤ እንዲሁም ችግኝ ሥራ እንደሆነ የሚያነሱት አቶ ብርሃኑ ይህ ሥራ በሚከናወንበት ወቅት ግን ውስንነቶች መኖራቸውን ያነሳሉ፡፡
አቶ ብርሃኑ እንደሚሉት እነዚህ ተግባራት በግለሰብ አባወራዎች ደረጃ ጭምር የሚከናወኑ እንደመሆናቸው ከመንግሥት መዋቅር ጋር በቅንጅት ያለመስራት ችግር አለ፡፡ የሚተከሉ ችግኞች በእንስሳት ምክንያት ለአደጋ መጋለጥ ሌላኛው ችግር ነው፡፡ እነዚህን እና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡

መላኩ ኤሮሴ

Published in ኢኮኖሚ

ኢሳ አል ማሄዳ በፊሊፒንስ በገበሬነት የነበራት ሕይወት ከባድ ነበር፡፡ ቢሆንም በእናት፣ በወንድሞቿና በቤተሰቦቿ መካከል ተከባ የነበረች ባቸው እነዚያ ወቅቶች መልካም እንደነበሩ ታስታውሳለች፡፡ ይሁንና ቤተሰቦቿን መርዳትና መደገፍ ስለምትፈልግ በ2006 በቤት ሠራተኛነት ወደ ዮርዳኖስ አቀናች፡፡ ቀጣሪዎቿም በወር 500 ዶላር ሊሰጡዋት ቃል ገቡላት፡፡ ይህም ቤተሰቦቿን ለመደገፍ በቂ ነበር፡፡
የአል ማሄዳስ መልማይ ኤጀንሲ ሥራ ያገኘላት ሶርያ ጠረፍ አቅራቢያ በሚኖሩ ዮርዳኖሳውያን ቤተሰቦች ውስጥ የነበረ ሲሆን፣ ሥራ ከጀመረች በኋላ በቤት ሥራው አሰልቺነት ተጠምዳ በአብዛኛው 17 ሰዓት በቀን በመስራት ትውል ነበር፡፡ በመጀመሪያው ወር 500 ዶላር ደመወዝ ተከፈላት፡፡ በቀጣዩ ወር 300 ዶላር ተሰጣት፡፡ ከዚያ በኋላ ገንዘቡ ቆመ፡፡ ቤተሰቡ የፋይናንስ ችግር እንደገጠመውና እንዳገኙ ወዲያው እንደሚከፍሏት የነገሯት ቢሆንም አልከፈሏትም፡፡ የቀጣሪዎቹ አታላይነትና ዘመናዊው ባርነቱ ከዚህ ይጀምራል፡፡
አል ማሄዳ የሥራውን ቦታ ለቃ መሄድ እንዳልፈለገች ትናገራለች፡፡ ምክንያቱም ወደ ውጭ መውጣት በጣም ስለምትፈራ ሀገሩን ስለማታውቀው የሚረዳኝ ሰው አገኛለሁ ብላ ስለማትገምትም ነው፡፡ በፍርሀት ተጠፍንጋ ኖራ የአሰሪዎቿን ቤት ጥላ ለማምለጥ የሚያበቃትን ድፍረት ለማግኘት ድፍን ዘጠኝ ዓመት ወስዶባታል፡፡
የመኖሪያና የሥራ ፈቃዷ ከተቃጠለ ዓመታት በመቆጠራቸው ቅጣት ተከማችቶባታል፡፡ የተቃጠለው አሰሪዎችዋ በመከልከል ሳይሰጧት በእጃቸው አስቀምጠውት ስለነበረ ነው፡፡ በእነርሱ ወንጀል በወቅቱ ባለመታደሱ እሷ ሕገወጥ ሆናለች፡፡ አሁን ዕድሜዋ 36 ነው፡፡ አል ማሄዳ ለሲኤንኤን ዘጋቢ እንባዋን እያዘራች እንደተናገረ ችው አሁን የቤት ሠራተኛ ሳትሆን አገልጋይ ባሪያ እንደነበረች ገብቷታል፡፡
የነበረችበትን ሁኔታ ስታስታውሰው በተኛችበት ቦታ በእንቅልፏም ያስበረግጋታል፡፡ ለቤተሰቦቿ ገንዘብ ለመላክ የነበራት ሃሳብ መምከኑ ምንም ለማድረግ አለመቻልዋ በጣም ከባድ ነገር ነበር፡፡
በዮርዳኖስ በአሰሪዎች መታለል የተለመደ ነው፡፡ የአል ማሄዳ ጉዳይ ብቸኛና የመጀመሪያ አይደለም፡፡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ስደተኛ ሠራተኞች በወቅቱ የሰሩበት ገንዘብ የማይከፈላቸው መሆኑን ጥቂቶች ከኮንትራት ጊዜው ማብቂያ በኋላ እንደሚከፍሉዋቸው ቃል በመግባት አሰሪዎቻቸው እንደሚያታልሏቸውና ቃላቸውን እንደማይጠብቁ በጣም ብዙ ማስረጃዎች አሏቸው፡፡
አንዳንድ አሰሪዎች ሠራተኞቻቸውን በቤት ውስጥ በመቆለፍ በቀን 20 ሰዓት በሳምንት ሰባት ቀን ሙሉውን ሥራ እንዲሰሩ በኃይል ያስገድዷ ቸዋል፡፡ ፓስፖርታቸውን ነጥቀው የትም እንዳይንቀሳቀሱ ማገድ የተለመዱ ድርጊቶች መሆናቸውን የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎቹ ይገልጻሉ፡፡
ይፋዊ በሆኑ የመንግሥት አሀዛዊ መረጃዎች መሰረት በዮርዳኖስ ውስጥ ከ50 ሺ በላይ የሚሆኑ ስደተኛ የቤት ሠራተኞች ይኖራሉ፡፡ ሌሎች ተገቢ መረጃ የሌላቸው ወደ 20 ሺ የሚገመቱ ስደተኞችም እንደሚኖሩ ይገምታሉ፡፡ ብዙዎቹ ሴቶች ወደ ዮርዳኖስ የሚገቡት ከደቡብ፤ ከደቡብ ምስራቅ እስያና ከምስራቅ አፍሪካ ነው፡፡ የወር ደመወዛቸው ከ200 ዶላር እስከ 500 ዶላር ይደርሳል፡፡ ሁሉንም ሥራ መስራት ይጠበቅባቸ ዋል፡፡ ከጽዳት እስከ ምግብ ማብሰል፤ልብስ መተኮስ፤አትክልት መንከባከብ፤ ሕጻናትን የመጠበቅና የመያዝ ሥራ ይሰራሉ፡፡
‹‹ደሕንነት እንዲሰማቸው ለማድረግ እንጥራለን›› ትላለች ለስደተኛ ሠራተኞች ሕጋዊ ድጋፍ ለማድረግ በ2007 ታምኪን በሚል ስም መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የመሰረተችው ሊንዳ አል ካላሽ፡፡ ጠበቆችን ካቀፈው ቡድኗ ጋር በመሆን አል ካላሽ በሠራተኛ ጉልበት ጥሰት፤ሠራተኞችን በአግባቡ ባለመያዝና በማንገላታት አሰሪዎችን በፍርድ ቤት እየከሰሰች በመርታት በርካታ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸውን ጉዳዮች አሸንፋለች፡፡ እኛ ባለን ልምድና ከራሳቸው ከሠራተኞች ጋር በመገናኘት እንዳየነው ስደተኛ ሠራተኞቹ ሁኔታውን ጥለው ለመውጣት ምንም ዓይነት መንገድ እንደሌላቸው ይሰማቸዋል ብላለች ሊንዳ አል ካላሽ፡፡
‹‹አንዳንዶቹ ስደተኛ ሠራተኞች ለማነጋገርም አስቸጋሪ ናቸው ይፈራሉ፡፡ በማንም ሰው ላይ እምነት የላቸውም፡፡ ደህንነት እንዲሰማቸው ለማድረግ እንጥራለን፡፡ ከእነሱ ጋር እጅ ለእጅ መጨባበጥ እና ማውጋት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ አንዳንዴም ማቀፍ ያስፈልጋል›› የምትለው ሊንዳ አል ካላሽ ይህም ብቸኝነት እንዳይሰማቸውና አንተም እነሱም በእኩል ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንዳላችሁ ስሜት እንዲፈጥርላቸው ይረዳል ትላለች፡፡
በ2010 (እ.ኤ.አ) አል ካላሽ ዘመናዊ ባርነትን በዮርዳኖስ በመዋጋት ላደረገችው ጥረት የአሜሪካን ስቴት ዲፓርትመንትን የሰዎች ዝውውር የጀግና ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከመንግሥት ኤጀንሲዎችና እንዲሁም ከሀገሪቱ የሕገወጥ ሰዎች ዝውውር ክፍል ጋር በቅርበት ትሰራለች፡፡ ይህ ድርጅት ከተቋቋመበት እ.ኤ.አ ከ2013 ጀምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጉዳዮችን በመመርመርና በማጣራት ተአማኒነትን ያገኘ ነው፡፡ የዮርዳኖስ መንግሥት ስደተኛ የቤት ሠራተኞችን በተመለከተ ችግር እንዳለ ይቀበላል፡፡ በኦፊሴል ደረጃ ግን የግለሰቦች ጉዳይ እንጂ በሰፊው የተዛመተ አይደለም ባይ ነው፡፡
የዮርዳኖስ መንግሥት ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎቹ መጠለያ አዘጋጅቷል፡፡ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት እ.ኤ.አ በ2017 ግለሰቦችን በሕገወጥ መንገድ በማዘዋወር ጉዳይ ባወጣው ዓለም አቀፍ ሪፖርት መሰረት ዮርዳኖስ ሕገወጥ የሰዎችን ዝውውር ለማስወገድ የተቀመጠውን አነስተኛ መመዘኛ ሙሉ በሙሉ ያላሟላች ሁለተኛዋ ሀገር ነች፡፡ ቢሆንም ትርጉም ያለው ለውጥ እያሳየች ነው፡፡ ራሱን የቻለ ጉዳዩን የሚከታተል ቡድን ከመፍጠር በተጨማሪ መንግሥት በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ ለሆኑ ሰዎች ዳር ካራማ የሚባል መጠለያ ከፍቷል፡፡ በዚህ ቦታ የቤት ሠራተኞች ጥገኝነት የሚሰጣቸው ሲሆን ጉዳያቸውም አብሮ ይመረምራል፡፡
ሱዛን ኮሽቤይ በዮርዳኖስ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የማህበራዊ ጉዳይ ሕገወጥ ሰዎችን የሚያዘዋውሩ ጉዳዮችን ክፍል በኃላፊነት የምትመራ ሲሆን፣ ለሲኤንኤን እንደገለጸችው ዳር ካርማ በተባለው ቦታ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ ለሆኑት ሰዎች የተቋቋመው ጣቢያ የመጀመሪያ ደረጃ ምላሽ ተደርጎ የሚታይ ነው ብላለች፡፡ በዚህ ስፍራ በቂ ቦታ ይሰጣቸዋል፤ ሁሉም ዓይነት አገልግሎቶች አሉ፡፡ ይህም በሥነልቦናና በአካል ማገገም እንዲጀምሩ ያደርጋቸዋል፡፡ የተሸከሙትን ከባድ የተጎዳ መንፈስና ለራሳቸው ዋጋ ያለመስጠት ስሜት እንዲያራግፉ የሚያስችል ችሎታ እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ እንዲሁም በድጋሚ የሕገወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎች ሰለባ እንዳይሆኑ ይረዳል ብላለች፡፡
አል ካላሽ እንደገለጸችው ስደተኛ ሠራተኞችን በተመለከተ ጆርዳን በመካከለኛው ምስራቅ ጥቂቶች ካላቸው በጣም ምርጥ የተባለው ሕግ አላት፡፡ በቅርብ ዓመታት ዮርዳኖስ የስደተኛ ሠራተኞችን መብት የሚጠብቅና የሚከላከል ሕግ አጽድቃለች፡፡ የሥራ ሰዓትን የወሰነ የሠራተኞችን የጉዞ መረጃ የሚይዙ አሰሪዎችን የሚቀጣ ሕግ አውጥታለች፡፡
እነዚህን ሕጎች ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም ሠራተኞች አቤቱታቸውን ይዘው ስለማይቀርቡ ከባድ ነው፡፡ ዮርዳኖስ በፀረ ሕገወጥ የሰው ዝውውር ላይ ያላትን ሕግ ለማሻሻል እየሰራች ሲሆን፤ በህገ ወጥ የሰው ዝውውር ላይ ወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ከባድ ቅጣትን ይጥላል፡፡
ብዙ ግፍና በደል በአስሪዎቿ የተፈጸመባት ስደተኛ የቤት ሠራተኛዋ አል ማሄዳ በሕዳር 2017 ወደ ፊሊፒንስ እንድትመለስ ተደርጎ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰራው ታምኪን የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት አሁንም ጉዳይዋን ይዞ ዓመታት በሚወስደው የዮርዳኖስ ፍርድቤት እየተከታተለው ይገኛል፡፡
የስደተኛ ሠራተኞች መብት ተከራካሪዋ አል ካላሽ ለስደተኛ ሠራተኞች መብት አንድ ጉዳይን በአንድ ጊዜ በመያዝ ሁኔታቸውን ለማሻሻል መዋጋትና መስራት መቼም እንደማታቆም ገልጻለች፡፡ ለእነርሱ ያለኝ መልዕክት ትላለች አል ካላሽ ‹‹መብታችሁን ጠይቁ ፤አሰሪዎቻችሁን አትፍሩ ፤መብቱ አላችሁ፤ ራሳችሁን አብቁ›› የሚል ነው፡፡

ወንድወሰን መኮንን

Published in ዓለም አቀፍ
Thursday, 08 February 2018 17:17

ያልተነበበው ሕገመንግሥት

ሕገመንግሥት የአንድ አገር እናት ሕግ ነው፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉት ሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነ ገዢ ሕግ ነው፡፡ የሀገሪቱን አጠቃላይ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የኢትዮጵያዊ ዜግነትን ምንነት፤ አንድ ዜጋ በየትኛውም የሀገሪቱ ክልሎች የመንቀሳቀስ ተዘዋውሮ የመስራት ሀብትና ንብረት የማፍራት በዜግነቱ ተከብሮ የመኖር መብቱ በሕገመንግሥቱ የተከበረለት መሆኑን አረጋግጧል፡፡
የሀገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ የመከላከያ፣ የደህንነት፣ የውጭ ፖሊሲ፣ የተፈጥሮ ሀብትና የመሬት አጠቃቀም በውልና በግልጽ ያሰፈረ በአጠቃላይ 106 አንቀጾች ያሉት ከዚህም ውስጥ ከቀድሞዎቹ ሕገመንግሥቶች በተለየ አንድ ሦስተኛው አንቀጽ ሰብዓዊ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚሸፍን ሕገመንግሥት ነው፡፡ ሕገመንግሥቱ አንድ ራእይ ነው ያለው፡፡ ራእዩ ዕድልና ተስፋን ይዟል፡፡ ራእዩ መዳረሻዎች አሉት፡፡
የፌዴራሉን ሕገመንግሥት መሰረት አድርገውና ተንተርሰው አግባብ ባለው ትርጉም ተመርኩዘው ነው ሌሎች ሕጎች ደንቦችና መመሪያዎች ሊወጡ የሚችሉት፡፡ ሹሞችም ዜጎችም በአግባቡ ሕገመንግሥቱን ያውቁታል አንብበውታል ማለት ግን አይደለም፡፡ አውቃለሁ የሚል ግን ሞልቷል፡፡ የሕግ ምሁራን የህግ ሰዎች ዳኞች ጠበቆች በስፋት ጠንቅቀው ያውቁታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ስለሌላው ለመናገር አፍ የለንም፡፡ «እንደው ዝም ነው እቴ አሉ እሜቴ ነው!» ነገሩ፡፡
አውላላ ሜዳ ላይ ሕዝቡን ለጭንቅና ግራ መጋባት ለትርምስ የዳረጉት ሕገመንግሥቱን ሳያውቁ ወይንም እያወቁ የጣሱት ሰዎች ሕገመንግሥቱን እናስፈጽማለን ብለው የግል ጥቅማቸውን ሲያሳድዱ መኖራቸው ነው፡፡ ለዚህ ነው ያልተነበበው ሕገ መንግሥት የምንለው፡፡ አውቆ ማጥፋትና ሳያውቁ ማጥፋት በሕግ ፊት እኩል አይሰፈሩም፡፡ ሳያውቁ በስህተትና በድፍረት የሰሩትን ሀጢያት ይቅር በላቸው በዚህ ቦታ ላይ አይሰራም፡፡ የሕግ ተጠያቂነት ያስከትላል፡፡ የተበደለው የሚበደለው ሀገርና ሕዝብ ነውና፡፡
በተግባር የታየው የኪራይ ሰብሳቢነት የሙስና የመልካም አስተዳደር፣ የዘረኝነት፣ የጎጠኝነት በፍትህ ሥርዓቱ ሂደት ዜጎች በዳኝነት አሰራር ላይ መማረራቸውን መግለጻቸው፤ በዜጎች ሰብአዊ መብት ላይ ሲደረግ የነበረ ጥሰት፤ ስልጣንን ያለአግባብ በማንአለብኝነት መጠቀም፤ ግለኝነት፤ ኔትወርክ በመዘርጋት የጥቅም መረብን ማስፋት፤መንግሥታዊ መዋቅሩንና የሥራና ኃላፊነት ቦታዎችን በቡድንና በኔትወርክ መያዝ የሌሎችን ዜጎች መብት ሲጥሱ ይታያል፡፡ ሌሎችም ያልዘረዘሩት የተከሰቱት ችግሮች ሁሉ በፌዴራል መንግሥቱ ሕገመንግሥት በግልጽ ሰፍረው የተደነገጉት አንቀጾች ሙሉ በሙሉ በመጣሳቸው የተከሰቱ መሰረታዊ ችግሮች ናቸው፡፡ ያልተነበበው ሕገ መንግሥት ያልነውም ለዚህ ነው፡፡
ሕገመንግሥቱን በውል ሳያውቁ ጥልቅ የሆነውንና በውስጡ ያካተታቸውን የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት አካል አድርጎ የተቀበላቸውን ታላላቅ አሕጉራዊና ዓለምአቀፋዊ ተቀባይነት እውቅና ያላቸውን ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንደ ማዕዘን ድንጋይ የሚቆጠሩትን ሕጎች እንዳሻው ይጥሳል፡፡ ሕገ መንግሥቱን በተግባር መሬት ላይ ሲደፍር በራሱ መለስተኛ አቅም ሲመነዝር የኖረ ባለስልጣን ሹም ካድሬ ለሕገ መንግሥቱ ጥብቅና ቆሜአለሁ ቢል አባቶች አንከትክቶ አሳቀኝ የሚሉት ዓይነት መሆኑ ነው፡፡
ይልቁንም «ቆመንለታል» የሚሉትን መንግሥት ተቀባይነቱ በሕዝብ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ያደረጉት መሰረቱን ያናጉት በሕገመንግሥቱና በድርጅት ታማኝነት ስም እየማሉ በጎሳና በዘር ጥላቻ ግን ተመርዘዋል፡፡ በሙሰኛነትና በኪራይ ሰብሳቢነት ታዛ ተጠልለው ሕዝብን ከህዝብ ሠራተኛን ከሠራተኛ ሲያጋጩ እንደግል ማጀታቸው በመቁጠር በሠራተኛው መብት ላይ ሲፈነጩ የነበሩ ሰዎች ናቸው ለሥርዓቱ ታላቅ አደጋን ያመጡት፡፡ ሕገመንግሥቱን የጣሱትም እነሱው ናቸው፡፡
ሥራ አስፈጻሚው በገባው ቃል መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ካለበትና መጸጸቱን በተግባር መለወጥ ካለበት ማራገፍ ያለበት የተሸከመውን በተሀድሶም ሊለወጥ ያልቻለውን በውስጡ የዘረኝነት መርዝ ፈልቶ የሚንተከተከውን በካድሬ ስም አዝሎት የኖረውን ህገመንግሥቱን በመጣስ ሕዝብና መንግሥትን ሆድና ጀርባ ያደረገውን ኃይል ነው፡፡ ሕገመንግሥቱን ጥሰውታል፡፡
ሕገመንግሥቱ በጣም ጥልቅና ሩቅ ነው፡፡ በሀገሪቷ ከጥንት እስከዛሬ ተፈጥረው የኖሩትን ያሉትን ብሔር ብሔረሰቦች የነበረባቸውን አድሎአዊና ኢፍትሀዊ ጭቆና እንዲወገድ ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር፣ ቋንቋቸው፣ባሕላቸው፣እምነታቸው፣ እንዲከበር የደነገገ፤ በየክልላቸው በመረጡት ይመራናል ባሉት እንዲተዳደሩ የራሳቸውን ክልላዊ ምክርቤት እንዲመሰርቱ ያስቻለ ነው፡፡
የአስተዳደር የትምህርት የጤና የግብርና የከተማ ልማት የፍትህ ቢሮ የፖሊስ ጥበቃና ሚሊሺያ እንዲኖራቸው አካባቢያቸውን የሕዝቡን ሰላምና ፀጥታ በቅርብ ሆነው ነቅተው እንዲጠብቁ ክልላቸውን የበለጠ ትኩረት ሰጥተው እንዲያለሙ የበለጠም እንዲሰሩ ያበቃ ሊከበር ሊጠበቅ የሚገባው ሕገመንግሥት ነው፡፡ በቅጡ ሥራ ላይ የሚያውለው ኃይል መጥፋቱ ነው ችግሩ፡፡
ሕገመንግሥቱ ታላላቅ ክልላዊና ሀገራዊ የመሰረተ ልማት ለውጦች በተጨባጭ እንዲመጡ ያደረገ ነው፡፡ አይደለም ሕዝቡ በስፋት ሊያውቀው ባለስልጣኖቻችን በየደረጃው ያሉ ሹሞች ሥራ አስኪያጆች፤ ምክትሎች፤ ጀኔራል ዳይሬክተሮች፤ የፖሊስና የፀጥታ ሹሞቻችን፤ የክልልና የቀበሌ ተመራጮቻችን በትክክል ሕገመንግሥቱን ጠንቅቀው ቢያውቁትና በሥራ ላይ ቢያውሉት ኖሮ ምንም ዓይነት ችግር በህብረተሰባችን ውስጥ አይፈጠርም ነበር፡፡
በሕገመንግሥቱ መሰረት መንግሥት ዜጎቹን የመጠበቅ፤የሕዝብ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ፤ መልካም አስተዳደር የማስፈን፤ብልሹ አሰራርን የመዋጋት፤ ባለስልጣን ሁነው ሕዝብን የበደሉትን በጥፋታቸው መጠን ለሕግ የማቅረብ፣የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚጥሱ የጣሱ ግለሰቦችን ለሕግ አቅርቦ የመቅጣት ሕገመንግሥታዊ ግዴታ አለበት፡፡ ይሄን አለመወጣት መንግሥትን በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ መሰረት ያስጠይቀዋል፡፡ ይሄንን በግልጽ ያሰፈረ መብትና ግዴታን የለየ ተጠያቂነትን ያስቀመጠ ሕገመንግሥት ነው ያለን፡፡
መልካም በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን የተፈጠሩ ችግሮች የሕዝብ ምሬትና በደል ገፍቶ መውጣት፤ የመልካም አስተዳደር፤ የሙስና የኪራይ ሰብሳቢነት፤ የዘረኝነት ችግሮች ሁሉ ሕገመንግሥቱን ሙሉ በሙሉ በመጣስና ባለማክበር የተነሳ የተፈጠሩ ስር የሰደዱ ችግሮች ናቸው፡፡ ልናርማቸው ልናስተካክላቸው ዳግም እንዳይደገሙ ለማድረግ ይቻላል፡፡ ሕዝቡ ሕገ መንግሥታዊ መብቱ ሳይጣስ ሳይሸራረፍ በአግባቡ እንዲከበር በሹሞች እንዳይጣስ በሰላማዊ መንገድ መታገል ሕገመንግሥቱ ያጎናጸፈው መብቱ ነው፡፡ያልተነበበው ሕገመንግሥት ደግሞ ደጋግሞ ሊነበብ ሊታወቅ ይገባል፡፡
ሕገመንግሥቱን ሕዝቡ በስፋት እንዲያውቀው የማድረግ ሥራ ጅምርና በአልፍ አገደም ደረጃ የሚታይ ቢሆንም በስፋት አልተሰራበትም፡፡ አንዱም ትልቁ ችግር ይሄ ነው፡፡ መሰረት የሌላቸው እንደ አውሎ ንፋስ የሰውን ስሜት የሚያናጉ መንገድ የለቀቁ ግርታና ብዥታ የሚፈጥሩ ብዙ ውዥንብሮች አሉ፡፡ ሕገመንግሥቱን ባሻቸው በታያቸው በመሰላቸው ለመተርጎም የሚከጅሉም አሉ፡፡
ሕገመንግሥቱ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የሁሉም ኢትዮጵያውን ዜጎች መብትና ጥቅም በእኩልነት እንዲከበር የቆመ ብዝሀነትን ያከበረ የሁሉም የጋራ የቃል ኪዳን ሰነድ ነው፡፡ ለምሳሌም ብንወስድ ሕገመንግሥቱ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያውያን ነው የሚለው፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች መብት በመከበሩ ክልላቸውን በነጻነት የመምራት የማስተዳደር የማልማት ባሕላቸውን ቋንቋቸውን እምነታቸውን የማሳደግ ሙሉ መብታቸውን የደነገገ ነው፡፡
ሕገመንግሥቱ ሰዎች እንደሚያወሩትና እንደሚገመቱበት ከየት እንዳመጡት በማይታወቅ መልኩ በመቃብራችን ላይ የሚለወጠው እንደሚሉት ዓይነትም አይደለም፡፡ ለዚህ ነው ያልተነበበ ሕገመንግሥት ነው የምንለው፡፡ ሳያውቁት ነው ስለ ሕገመንግሥቱ የሚያወሩት የሚናገሩት፡፡ ይሄ ደግሞ ያሳፍራል፡፡ ሕሊና ካላቸው ሊያፍሩም ይገባል፡፡ ሕገመንግሥቱ ያላለውን ከኪሳቸው እያወጡ የሚሉ ናቸውና፡፡
ሕገመንግሥት በሕዝብ አብላጫ ድምጽና ይሁንታ በሕዝበ ውሳኔው(በሪፈረንደም) መሰረት የተቀመጠለትን ሥርዓት ተከትሎ ሊሻሻል ይችላል፡፡ ስልጡንና ዘመነኛ ዓለምአቀፍ ልምዶችን እውነቶችን ሁሉ ያካተተ ሕገመንግሥት ነው፡፡ ያልተነበበው ወይም በቂ ግንዛቤ እንዲያዝበትያልተደረገው ሕገመንግሥት ነው የምንለውም ለዚህ ነው፡፡
በዚህም መሰረት ሕገመንግሥቱ በአንቀጽ 105 ሕገመንግሥቱን ስለማሻሻል በሚለው ርእስ ስር ባስቀመጠው መሰረት ሀ/ ሁሉም የክልል ምክርቤቶች የቀረበውን ማሻሻያ በድምጽ ብልጫ ሲያጸድቁት ለ/ የፌዴራል መንግሥቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ ማሻሻያውን ሲያጸድቀው እና ሐ/ የፌዴሬሽኑ ምክርቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ ማሻሻያውን ሲያጸድቀው ነው ይላል፡፡
ይህንን የመሰለ ዘመንኛ ሀገራዊ አንድነትን በመከባበር ላይ የተመሰረተ አብሮነትን የሕዝብ የበላይነትን የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን መከበርን ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍልን የደነገገ ሕዝብን የበደለ የዘረፈ በሕገመንግሥቱ መሰረት በሕግ እንዲጠየቅ የደነገገ ሕገመንግሥት ነው ያለን፡፡ያልተነበበው ሕገ መንግሥት ሊነበብ ሊታወቅ የሚገባው የሕዝብን መብትና ነጻነት እንዲከበር እንዳይጣስ የደነገገ በመሆኑ ነው፡፡
የተፈጠሩት ችግሮች ሁሉ የተፈጠሩት ሕገመንግሥቱ በአግባቡ በሥራ ላይ ባለመዋሉና በአስፈጻሚዎች ሕገወጥ ጥሰት የተነሳ ነው፡፡ ፈጥኖ ማረም ያልተነበበውን ሕገ መንግሥት ሁሉም እንዲያውቀው በሥራ ላይ እንዲያውለው እንዲጠብቀው ለሕዝብም ለራሱ ለመንግሥትም ነው፡፡ ያልተነበበው ሕገመንግሥት በሁሉም ዘንድ ይነበብ፡፡

Published in አጀንዳ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።