Items filtered by date: Friday, 09 February 2018

በ1950ዎች መብራት ሃይል የእግር ኳስ ቡድን በመባል የተመሰረተው የአሁኑ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ አገሪቱን በስፖርት ዘርፍ ለማገዝና በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች አገርን ወክለው ሊሳተፉ የሚችሉ ብቃት ያላቸው እግር ኳስ ተጫዋቾችን ማፍራት አንዱ የቡድኑ ግብ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሠራተኛው ብሎም ወጣቱ በአካልና በአእምሮ የዳበረ እንዲሆን፣ በስነ-ምግባር የታነጸ ስፖርት ወዳድ ዜጋ እንዲፈጠርና ስፖርቱ በአገሪቱ እንዲያድግ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ አበረታች ስራዎችን ሰርቷል፡፡ ከአምስት አስርት አመታት በፊትም ቡድኑ የወቅቱ አንጋፋ ከነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊስና መቻል ቡድኖች ጋር ተወዳዳሪ እንደነበር መረጃዎች ይዘክራሉ፡፡
የድርጅቱን ሠራተኞች ጨምሮ ከልዩ ልዩ ትምህርት ቤቶችና የስፖርቱ እውቀት እንዲሁም ልምድ ባላቸው ግለሰቦች ስብስብ የተመሰረተው የኤሌክትሪክ እግር ኳስ ቡድን በ1954ዓ.ም በሁለተኛ ዲቪዚዮን ተመዝግቦ የሸዋ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሚያዘጋጀው ውድድር ላይ ተሳታፊ ሆነ፡፡ በውድድሩም አጥጋቢ ውጤት በማስመዝገብ በ1955ዓ.ም ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን በመሸጋገር የታዋቂነት ምዕራፉን አሃዱ ማለት ቻለ፡፡
ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በታሪክ አጋጣሚም እንደ ፍቃደ ሙለታ፣ መሐመድ ሀሰን፣ መሐመድ አሊ እና ሌሎች ስመጥር ስፖርተኞችን ማፍራት የቻለ ቡድን ነው፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ1958ዓ.ም የሚሊቴሪ ቡድንን ከሲቪል ቡድን ለመለየት በወሰደው እርምጃ ኦሜድላ፣ መቻል፣ አየር ኃይልና ክቡር ዘበኛን ከውድድር ሲያስወጣ የኤሌክትሪክ ቡድን ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ ከመቻልና ከኦሜድላ ጠንካራ ተጫዋቾችን በመውሰድ ከ1958ዓ.ም ጀምሮ ጊዮርጊስ ቡድን ጋር ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን በቃ፡፡
ከክለቡ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየውም፤ በወቅቱ የነበረው የውድድር ዘመን የዋንጫ ባለቤት የሚሆነው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ሲሆን፤ የኤሌክትሪክ ቡድን አብዛኛውን ውድድር በሁለተኛነት ያጠናቅቃል፡፡ ይህም የቡድኑን ጥንካሬ ምን ያህል እንደነበር የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህ ወቅት በአገር ውስጥ በተካሄደው ውድድር የአመቱ ኮኮብ ግብ ጠባቂ በመሆን የዋንጫ ተሸላሚ የነበረው ጠንካራ በረኛ አምደሚካኤል ለብሄራዊ ቡድን ለመመረጥ ችሏል፡፡
በ1962ዓ.ም አጋማሽ ላይ በመጣው የውጤት መውረድ ምክንያት በጊዜው የነበረው ኮሚቴ በቡድኑ ውስጥ የአቋም ለውጥ ማድረጉም አይዘነጋም፡፡ በዚህም ክለቡ በ1963ዓ.ም ከታዳጊ ወጣቶች ተተኪ ስፖርተኞችን መልምሎ የኢትዮጵያ የጥሎ ማለፍ ሻምፒዮን በመሆን የመጀመሪያ ዋንጫ ለማግኘት ችሏል፡፡ የውድድር አመቱን በድል ያጠናቀቀው የኤሌክትሪክ ቡድን በቀጣዩ ዓመት ማለትም በ1964 ዓ.ም የኤርትራውን እምባይሰራ ቡድን በማሸነፍ ለሁለተኛ ጊዜ የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ሻምፒዮን ለመሆን በቅቷል፡፡ በዚህ ጨዋታ የኤሌክትሪክ ቡድንን በመጨረሻው ደቂቃ ለአሸናፊነት ያበቃችው የመሀመድ አሊ ተአምራዊ ጎል አትዘነጋም፡፡
በኮርፖሬሽኑ የስፖርት ክለብ ታሪክ ወርቃማው ዘመን የሚባለው ይህ ወቅት የባለስልጣኑ አመራሮች ለክለቡ አሰልጣኞችና ተጫዋቾች የመጀመሪያውን ሽልማት ያበረከቱበት እንደነበር ይታወሳል፡፡ ክለቡ በዚህ ጉዞው የአሸናፊነትና የጸባይ ዋንጫዎችን ከማንሳቱ ባሻገር ለብሄራዊ ቡድን በርካታ ተጨዋቾችን መመገብ የቻለም ነው፡፡
ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በውጤትና በጠንካራ ተፎካካሪነቱ ቢቀጥልም እያደር ለዝቅተኛ ውጤት እጅ መስጠቱ አልቀረም፡፡ በዘንድሮ ዓመት ውድድር እንኳ እስካሁን ባደረጋቸው ጨዋታዎች በ16ኛ ደረጃ የፕሪሚየር ሊጉ ግርጌ ላይ ተቀምጧል። ለመሆኑ ቡድኑን ከአንጋፋነቱ ምን አራቀው? ውጤት እያጣ የመጣውስ ለምንድን ነው? ወደቀድሞ ስሙ ለመመለስና ጠንካራ ተፎካካሪ ለማድረግስ ምን እየተሰራ ነው? ክለቡ ከወራጅ ቀጣናስ ይወጣ ይሆን? የሚሉትንና ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከቡድኑ ስራ አስኪያጅ አቶ ለገሠ ኩሳ ጋር ያደረግነው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናክሯል፡፡
አዲስ ዘመን፦ ቡድኑ ውጤት ያጣባቸው ተጨባጭ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
አቶ ለገሠ፦ በዋናነት ውጤት ያጣበት ምክንያት በተጫዋቾች ላይ የሚስተዋለው የስነ-ልቦና ችግር ነው፡፡ ተጫዋቾቹ በብዛት ውጤት ለማምጣት ሳይሆን ከወራጅ ቀጣና ላለመውረድ የሚጫወቱበት ሁኔታ መኖር አንዱ ተግዳሮት ነው፡፡ ሌላው የአቅም ማነስና በጨዋታ ላይ በሚከሰቱ መዘናጋቶች አሉ፡፡ ከዚህ አኳያ በቡድኑ የጨዋታዎችን ትንታኔ የሚሰሩና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ጨዋታዎችን የመተንተን አቅም ያላቸው ባለሙያዎች ያሉ ሲሆን፤ በጨዋታ ትንተና ወቅት የመጀመሪያው ስራ ችግሩን ለይቶ ማወቅ ነው፡፡ በእዚህም መሰረት ሁሉም ባለሙያዎች የሚስማሙበት የትንተና ውጤት በቡድኑ አብዛኛው ጊዜ ግብ የሚቆጠርበት በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ ክፍለ ጊዜ ሲሆን፤ ይህም በተጫዋቾች ላይ በሚፈጠሩ መዘናጋቶችና በአቅም ማነስ ችግር ነው፡፡
አዲስ ዘመን፦ የአቅም ማነስ ብቻውን ለውጤት ማጣት ምክንያት ይሆናል?
አቶ ለገሠ፦ የአቅም ማነስ ብቻውን የውጤት ማጣት ችግር ባይሆንም የተጫዋቾች ሥነ-ልቦናዊ ዝግጅት ማነስም አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ሌላው ከነባሩ አሰልጣኝ ወደ አዲሱ አሰልጣኝ የኃላፊነት ሽግግር ሲደረግ የራሱ የሆነ ችግር ያስከትላል፡፡ እግር ኳስ የብዙ ነገሮች ስብስብ ውጤት በመሆኑ አንዱ ከጎደለ ሌላውን ይዞት ይጠፋል፡፡ ይህን ችግር ለመቀነስና በስፖርተኞቹ ላይ የስነ-ልቦና ስራ ለመስራት ከሌላ ቦታ የስነ-ልቦና ባለሙያዎችን በማምጣት እንዲያስተምሩ እየተደረገ ነው፡፡ አሰልጣኝ ሲቀየርም ሁለቱንም አሰልጣኖች በየግል በማናገር ያደረጉት የኃላፊነት ርክክብ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መከናወኑን ተዋቾቹ ፊት እንዲያሳዩ ተደርጓል፡፡
አዲስ ዘመን፦ ቡድኑ ካለበት የውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ ለማውጣት የእርሶ ድርሻ ምን ነበር?
አቶ ለገሠ፦ መብራት ኃይል በጣም የምወደው ክለብ ነው፡፡ የክለቡ ውጤት የማሽቆልቆል ጉዳይም ሁል ጊዜ ከራሴ ጋር እንድሞግት ያደርገኛል፡፡ ምክንያቱም ማሊያውን ለብሼ ተጫውቻለሁ፤ ክለቡም ለእኔ ብዙ ነገር አድርጎልኛል፡፡ የአቅርቦት ኃላፊ ሆኜ እየሰራሁ ሳለ ክለቡ ለምን ውጤት አጣ የሚለው ነገር ቁጭት ፈጠረብኝ፡፡ ከዚያ በመነሻነትም አንዳንድ መጠይቆችን አዘጋጀሁ፡፡ ከታችኛው ዲቪዝዮን መጥተው በአንድ ጊዜ ውጤታማ መሆን የቻሉትን ክለቦች ተሞክሮ ለመቀመርና ቡድኑ እንደሌሎቹ ለምን አይሆንም የሚለውን ሀሳብ ማጠናቀር ያዝኩ፡፡ ፈጣን ለውጥ ለማምጣትም ምን መደረግ አለበት የሚል ሀሳብ ለቦርዱ አቀረብኩ፡፡ በቀጣይ ቡድኑን ካለበት ውጤት ማጣት የሚታደጉ እቅዶችን ከቦርዱ አባላትና ቴክኒክ ኮሚቴ ጋር ወደ ተግባር በመቀየር፣ የተጫዋቾችን ስነ-ልቦና በማጎልበትና አቅም መገንባት ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ከችግሩ ለማውጣት የበኩሌን ሃላፊነት እወጣለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቡድኑ ውጤት እያጣ መሆኑን ስትገነዘቡ ችግሩን ለመፍታት ምን መፍትሄ አስቀመጣችሁ?
አቶ ለገሠ፦ ወደ ቡድኑ አመራርነት የመጣሁት ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ ሲሆን፤ የቡድኑን የውጤት ማሽቆልቆል የተረዳሁትም በመጣሁበት ወቅት ነው፡፡ ወደ ኃላፊነቱ እንደመጣሁ የቡድኑን አፈጻጸም ስመለከት ቡድኑ ያደረጋቸው የቅድመ ዝግጅት ውድድሮችን ማድረግ ከሚገባው አኳያ አነስተኛ ነበሩ፡፡ ለአብነት የወዳጅነት ጨዋታዎች ምን ያህል አደረገ ብዬ ስመለከት ሶስት ጊዜ ብቻ ማድረጉን ተገነዘብኩ፡፡ ይህም ቅድመ ዝግጅት ወቅት ላይ ብዙ አለመስራቱን ያመላክታል፡፡ በዚህም ባደረጋቸው የወዳጅነት ጨዋታዎች ውጤቱስ ምን ይመስላል የሚለውን ሳጤነው ሶስቱንም እኩል በሆነ ውጤት መውጣቱን አረጋገጥኩ፡፡ ስለዚህ ከልምድ እንደተረዳሁት ለአንድ የእግር ኳስ ቡድን በዝግጅት ወቅት የሚደረገው የወዳጅነት ጨዋታ ከ8 እስከ 11 ጊዜ መደረግ ሲኖርበት ኤሌክትሪክ ግን በጊዜው ሶስት ጨዋታዎችን ብቻ አድርጎ ወደ ውድድር መግባቱ ለአሁኑ ውጤት ማጣት ተጠቃሽ ምክንያት ነው፡፡
በተጨማሪም በወዳጅነት ጨዋታ ወቅት የነበረውን የቡድኑን አፈጻጸም ብንመለከት ጎል ሲገባበት አልተስተዋለም፤ ጎልም ሲያስቆጥር እንደዚያው፡፡ ጎል ማግባት ካልተቻለ ደግሞ ደረጃን ከፍ ማድረግ አይቻልም፡፡ በተመሳሳይ በየጨዋታዎቹ ግብ ሲቆጠርበት የነበረው በአብዛኛው ከቅጣት ምት ጀምሮ ቢሆንም ቡድኑን ወደ ዝቅተኛ ደረጃ አምጥቶታል፡፡ ሆኖም ቡድኑ ጥሩ ቡድን አልነበረም ብሎ ለመናገር የሚያስደፍረኝ ምክንያት የለም፡፡ ምንም እንኳን ነጥቦችን እንደሚፈለገው ባያመጣም ጥሩ የእግር ኳስ አጨዋወት የሚያሳይ ቡድን ነው፡፡ በእግር ኳስ አጨዋወት ተሰጥኦ የዳበሩ ተጫዋቾች ነበሩት፡፡ ይህንን በተመለከተ አሰልጣኙንም አስተያየት እንሰጠው ነበር፡፡ እገዛም እናደርግለት ነበር፡፡ በዚያ መሰረት ስንሰራ ቆይተናል፡፡
አዲስ ዘመን፦ ለአንድ ቡድን ውጤታማነት ምን ያስፈልጋል ብለው ያምናሉ? እናንተስ በምን መልኩ እየሰራችሁ ነው?
አቶ ለገሠ፦ በመጀመሪያ ቁርጠኛና ራእይ ያላቸው ተጫዋቾች ያስፈልጋሉ፡፡ ከሚከፈላ ቸው ገንዘብ እኩል ሊያገልግሉም ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ የሚጀመረው ከምልመላ ነው፡፡ ትክክለኛው የተጫዋቾች ምልመላም የሚጀመረው ከአሰልጣኙ ነው፡፡ በእኛ አሰራር አሰልጣኙ ለምልመላ ያቀረባቸውን ተጫዋቾች ቴክኒካል ኮሚቴ ያቀርባል ከዚያም ወደ እኔ ይመጣል፡፡ እኔ ለቦርድ እጽፋለሁ፤ ቦርዱ ከአሰልጣኝ ለሚነሳው የተጫዋች ማንነት ራሱን ችሎ ለሚሰራው የድርድር ኮሚቴ ያቀርባል፡፡ ኮሚቴም ያመነበትን ተጫዋች የዋጋ ድርድር ያደርጋል፡፡ ከዚያም ቴክኒካል ኮሚቴ ስታፉና እኔ አንድ ላይ ሆነን ኮንትራቱ እንዲፈረም አድርገን ለፌዴሬሽን እናሳውቃለን፡፡ በዚህ መሀል በአሰልጣኙ የምልመላ እጩ ውስጥ ቀርበው ከሌሎች ቡድኖች የተሻለ ክፍያ ሲያገኙ የሚሄዱ ተጫዋቾችም አሉ፡፡ በዚህ መልክ ነው የተጫዋች ግዥ ስንፈጽም የነበረው፡፡ ከዚያም በቀጥታ ወደ ዝግጅት ነው የምናመራው፡፡
ለአንድ ክለብ መጠናከርና ውጤታማነት ከተጫዋቾች ቀጥሎ ትልቁ አስፈላጊ ነገር ራእይ ያለው ቁርጠኛ የሆነ አሰልጣኝ ነው፡፡ በዚህ አይነት ቡድኑ ውጤታማ እንዲሆን ይረዳ ዘንድ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ያሰለጠኑና ትልቅ ልምድ ያላቸው አዲስ አሰልጣኝ ማምጣት ችለናል፡፡ እርሳቸውም ትጉህ ታታሪ አሰልጣኝ እንደሆኑ በቅርበት እያየሁ ነው፡፡
በሶስተኛ ደረጃ ልምድ ያለው የቴክኒካል ስታፍ ያስፈልጋል፡፡ እኛ ጋር ያሉት የቴክኒክ ስታፍ ባለሙያዎች ይህንኑ ያሟሉ ናቸው፡፡ ከቡድኑ ጎን በመቆም የሚችሉትን ሁሉ አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡ ስለዚህ በዚህ በኩል ጎደለ የምለው ነገር የለኝም፡፡
አዲስ ዘመን፦ ቡድኑን ዋጋ እያስከፈሉ ያሉት ነገሮች ምንድን ናቸው?
አቶ ለገሠ፦ ግብ አለማስቆጠራችን ዋጋ እንድንከፍል ከሚያደርጉን ነገሮች አንዱ ነው፡፡ ግቦች የሚገኙት በጭንቅ ነው ግን እነርሱንም አንጠቀምበትም፡፡ በመጀመሪያው ግማሽና በሁለተኛው ግማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ላይ የምናገኛቸው ያለቁ እድሎች ሳንጠቀምባቸው ቀርተናል፡፡ ነገር ግን እኔ የማስበው በእግር ኳስ ዋናው ስራ ግቡ ጋር መድረስ ሲሆን፤ ግብ የማስቆጠር እድልን ሳይጠቀሙ መቅረት ደግሞ ትልቅ ዋጋን ያስከፍላል፡፡ እኛም ግብ ጋር መድረስ የሚችል ቡድን ገንብተናል፡፡ ቢሆንም የግብ አጋጣሚዎችን ሳንጠቀምባቸው የቀረን ጊዜያት አሉ፡፡ ሌላው ዋጋ የሚያስከፍለን ነገር የኳስ ቅብብሉ ቀጥተኛነት ነው፡፡ በእርግጥ በመሯሯጥ ኳስ መንጠቅ ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን በትክክል ለሰው ማድረስ ካልተቻለ አደጋ ነው፡፡ ይህንንም በየጊዜው እንወያይበታለን፡፡
አዲስ ዘመን፦ በመንግስት በጀት የሚታዳደሩ ክለቦች ህዝባዊ መሰረትነት ይጓላቸዋል ከሚል ሀሳብ በመነጨ ክለቡ ውጤት በማጣቱ የመፍረስ እጣፋንታ ሊኖረው ይችላል የሚል የስፖርት ቤተሰቡ ግምታዊ አስተያየት አለ፡፡ እርሶ ይህንን እንዴት ያዩታል?
አቶ ለገሠ፦ በመንግስት በጀት የሚተዳደር ክለብ እጣፋንታው የሚወሰነው በመንግስት ነው፡፡ አንድ ግለሰብ ብቻውን የሚወስንበት አይደለም፡፡ እኔ የተቀጠርኩበትን ኃላፊነቴን እወጣለሁ፡፡ ክለቡ አንጋፋ ክለብ ነው፤ በእኔ በኩል እንዲፈርስ አልፈልግም፤ ይፈርሳል የሚል እምነትም የለኝም፡፡ ምክንያቱም መብራት ኃይል እግር ኳስን ብቻ አይደለም ይዞ የሚንቀሳቀሰው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ታዋቂ የሆኑ የአትሌቲክስ፣ የብስክሌት፣ የጠረጴዛ ቴኒስ ቡድኖች አሉን፡፡ በእነዚህ ውስጥ የታቀፉ በርካታ ውጤታማ ስፖርተኞችም አሉን፡፡ የእግር ኳስ ቡድኑም ቢሆን የወደፊቱን ብሩህ ጊዜ እንድናይ ያደርገናል እንጂ የመፍረስ አዝማሚያ ይታይበታል ብዬ አላስብም፡፡
የሌላው ቡድን መፍረሱ የራሳቸው ምክንያት ይኖራቸዋል፤ በእኛ በኩል ክለቡን በብቃት የሚመሩ ጥሩ አመራሮች፣ በስነ-ልቦና የዳበሩ ቁርጠኛ ተጫዋቾች፣ ባለ ራእይ አሰልጣኞች እስካሉ ድረስ ቡድኑ ይፈርሳል ብሎ ለመናገር አያስደፍርም፡፡ በእርግጠኝነት ከፊታችን ባሉት ነገሮች ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥተን ሁላችንም ደስተኞች እንደምንሆን ነው የማስበው፡፡
የፋይናንስ ምንጮችን በተመለከተ የተለያዩ አጋር ድርጅቶችንና ሌሎች አካላትን ስፖንሰር የመፈለግ ስራዎችን እንሰራለን፡፡ በእርግጥ የእነዚህን ድጋፍ ለመጠየቅ የያዘን ነገር ቢኖር ውጤቱ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ፦ የቡድኑ ተጨባጭ እቅድ ምንድነው?
አቶ ለገሠ፦ እግር ኳስ የማሸነፍ ጨዋታ ነው፡፡ ይህ እንደ ህግ የተቀመጠ ሳይንሳዊ ትምህርት ነው፡፡ ስለዚህ ደረጃ አስጠብቆ መውጣት የሚል እቅድ ዓላማ መሆን አይችልም፡፡ ይህ ከሆነ ከእግር ኳስ ፍልስፍና የተለየ እቅድ ነው፡፡ በእርግጥ ከፊት ባሉት ነገሮች እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ እያንዳንዷ ጨዋታ ለእኛ የዋንጫ ጨዋታ ናት በሚል እሳቤ ነው የምንቀሳቀሰው፡፡ ምክንያቱም እኔ የአስተዳደር አካል ሆኜ ስንቀሳቀስ የሚወጣው ወጪ ይቆጨኛል፡፡ እስከ ዋንጫ ለመጓዝ እቅድ አለን፡፡ በእርግጥ ያጣናቸው ነገሮች ይጎትቱናል፡፡ ሆኖም እቅዳችን መቶ በመቶ እስከ መጨረሻው ድረስ ተፋልመን ውጤቱን ቀልብሰን አንድ ነገር ጨብጠን ለመውጣት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፦ እቅዱን ለማሳካትስ በአሰልጣኞችና በተጫዋቾች በኩል ያለው መነሳሳት ምን ይመስላል?
አቶ ለገሠ፦ በቡድኑ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች አሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከታዳጊዎች የሚቀላቀሉም አሉ፡፡ በመሆኑም የአሰልጣኝ አሸናፊን ልምድ ተጠቅመን ብዙ ስራ በተጫዋቾቹ አዕምሮ ላይ እንዲሰራ ይደረጋል፡፡ ሁሉንም ወደ አንድ አስተሳሰብ በማምጣት የቡድን መንፈሱ እንዲጠነክር እየተደረጉ ያሉ ስራዎች አሉ ቀጣይነት ባለው መልኩም ይህ ይሰራል፡፡ ጠንካራው የቡድን መንፈስም ወደ አሸናፊነት መንፈስ መለወጥ እንደሚገባ ታሳቢ ይደረጋል፡፡ ሁሉም የቡድን አባል በእኔነት ስሜት መስራት እንዳለባቸው ይገነዘባሉ፡፡ አሁን በቡድኑ ውስጥ እየታየ ያለውም ይኸው ነው፡፡ እርስ በእርሳቸው እየተሰባሰቡ በስህተቶቻቸው ዙሪያ ይነጋገራሉ፤ ይተራረማሉ፡፡
አዲስ ዘመን፦ የቡድኑ የወደፊት ስጋቶች ምንድን ናቸው?
አቶ ለገሠ፦ ውጤት ለማግኘት ካለን ፍላጎት አንጻር በአብዛኛው የአጭር ጊዜ ስራዎች ላይ ነው ትኩረት እናደርጋለን፡፡ ወደፊት ምን እናድርግ የሚለውን አለማሰባችን እንደ ስጋት እቆጥራለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን ለወደፊት አናስብም ማለት አይደለም፡፡ እያንዳንዷ ጨዋታ ለእኛ የዋንጫ ጨዋታ ተደርጋ ስለምትቆጠር ትኩረታችን ወደዚህ ያዘነበለ ይሆናል፡፡ ከዚህም የተነሳ ቁርጠኝነትን እንዳናጣ እሰጋለሁ፡፡ ከዚህ ውጭ ብዙ ስጋት አለ ብዬ አላስብም፡፡
አዲስ ዘመን፦ የውጪ ተጫዋቾች ግዥ የሚፈጸመው በምን አግባብ ነው?
አቶ ለገሠ፦ ተጫዋቾችን የሚያቀርቡ ወኪሎች አሉ፡፡ በዚህ መሰረት የሚያቀርቡ ተጫዋቾችን ማንነትና አቅም በተንቀሳቃሽ በምስል በተደገፈ ሁኔታ ያቀርቡልናል፡፡ የቀረበውንም ተጫዋች በቅድሚያ አሰልጣኞች በመቀጠልም የቴክኒክ ቡድኑ፣ ቀጥሎ ስራ አስኪያጁ ከዚያም ቦርዱና የድርድር ኮሚቴ በሰንሰለት ተዋቅረው ተፈላጊ የሆኑ ተጫዋቾች እንዲመረጡ ይደረጋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በቡድኑ ሁለት የውጭ ተጫዋቾች የሚገኙ ሲሆን፤ የተመረጡትም በዚሁ መንገድ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ጊዜዎትን ሰውተው ለሰጡኝ ማብራሪያ በጣም አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ለገሠ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አዲሱ ገረመው

Published in ስፖርት
Friday, 09 February 2018 18:11

ሰሚ የሌለው መልዕክት

መቼም ዓይን አላይም፤ ጆሮ አልሰማም፤ አይልም። ሰምተንም ሆነ አይተን የምንታዘበው ብዙ ነው፡፡አንዳንዱ ግን በዋዛ የምናልፈው አይደለም። በተለይ ለይምሰል የሚሠሩ ሥራዎች ያስቆጫሉም፤ ያበሳጫሉም። በተደጋጋሚ እያየሁ የሚያበሳጨኝ ህብረተሰቡ እንዲያውቃቸው በጎዳና ላይ ሰሌዳዎች አማካኝነት በጽሁፍ የሚተላለፉ መልዕክቶችና በመሥሪያ ቤቶች ደጃፍ ላይ የሚለጠፉ እራስን የማስተዋወቂያ ዘዴዎች ናቸው፡፡መልዕክቶቹ የሚለጠፉት ጽሁፉን የሚፅፈው እውቅ ፀሐፊ ተፈልጎ፣ ጽሁፉ ለሚሰፍርበትም ከፍተኛ ገንዘብ ወጥቶበት ነው፡፡
እውቁ ባለሙያ የተጠበበት ጽሁፍና ከፍተኛ ገንዘብ የወጣበት የጽሁፍ ማስፈሪያው የታለመለትን ግብ ሳያሳካ ትርፉ ተመልካቹን ወይም አንባቢውን በማስቆጨቱ ነው ብዕሬን ያነሳሁት፡፡ በተደጋጋሚ በምጠቀምበት በመንገዴ ላይ መሆኑ ደግሞ ከመልዕክቱ ጋር እፋጠጣለሁ፡፡ ዓላማው መልዕክት ማስተላለፍ ስለሆነ መልዕክት እለዋለሁ እንጂ በዚህ ደረጃ የሚገለፅ አልነበረም፡፡ በአጋጣሚ ያየኋቸው መልዕከቶች ተመሳሳይ ይዘት አላቸው፡፡ልዩነታቸው በተቋም ደጃፍ እና በጎዳና ላይ መለጠፋቸው ነው፡፡ የምላችሁ ተቋም በሀገሪቷ ብቸኛና እድሜ ጠገብ ፋበሪካ ነው፡፡ በተቋቋመበት ዘመን ዳር ወይም ከከተማ ወጣ ባለ አካባቢ የተገነባ ነው፡፡ አሁን ግን መሀል ከተማ ላይ ሆኗል፡፡ ታዲያ ፋብሪካው ወደሚገኝበት አካባቢ ሲሄዱ ሥፍራው መድረስዎን የሚያውቁት ከሚያመርተው ምርት በሚወጣው ጠረን ነው፡፡
በተለይ ጠረኑ የሚታወቀው ይህ ፋብሪካ በሽታው ብቻ ሳይሆን፣ ከአንደኛው የምርት ክፍሉ ይሁን ከሌላ ቡልቅ ቡልቅ የሚለው ጥቁር ጢስ መጨመሩ የአካባቢ ጥበቃው ነገር ያሳስባል፡፡ ለነገሩ ፋብሪካው በመግቢያው በር ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት እንደሚሰጥ ጎላ ባለ ጽሁፍ ለጥፏል፡፡ መልዕክቱና ተግባሩ አለመጣጣሙ ሁሌም ጥያቄ ይፈጥርብኛል፡፡
በተመሳሳይ የተገረምኩበትም፤ ያስቆጨኝም የቆሻሻ ክምር ያለበት፡፡ የሚወርደው ውሃ ወደ አረንጓዴ ቀለም ተቀይሮ ለእይታ የሚያስጠላና ለጤናም አሳሳቢ በሆነ ብዙ ህዝብ በሚተላለፍበት እንዲሁም የተለያዩ ማህበራዊና ህዝባዊ ክንውኖች በሚፈፀሙበት ሥፍራ በሚገኘው ወንዝ በፊት ለፊቱ በጉልህ «ወንዞቻችንን ከብክለት እንከላከል» በማለት የሚነበበው መልዕክት ግርም ብሎኝ ነው፡፡ ይህ የጎዳና ላይ መልዕክት ህዝብ እንዲያውቀው ከተደረገ ጊዜያቶች ተቆጥረዋል፡፡ ግን «ቄሱም ዝም፣ መጽሐፉም ዝም» እንደተባለው ሰሚ የሌለው መልዕክት ሆኗል፡፡
ለነገሩ እንዲህ ያሉ ጆሮ ዳባ ልበስ አይነት ነገሮች እየተለመዱ ነው ልበል፡፡ ወቅታዊ የሆኑ መልዕክቶች ለህዝቡ እንዲደርሱ በማሰብ ለምሳሌም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሠረት ድንጋይ የተጣለበት ቀን ሲከበር ወይም ደግሞ አንድ ተቋም በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ አውደ ጥናት ሲያዘጋጅ በነጭ ባነር ላይ በትልቁ መፈክር መሰል መልዕክቶችን ለማስተላለፍ የተሰቀለው አውራጅ አጥቶ ረጅም ጊዜ ማስቆጠሩ ኃላፊ አግዳሚውን የሚያስገርም ነው፡፡ እነዚህ በህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የሚሠሩ ሥራዎች ሲደጋገሙ ይስተዋላሉ፡፡ እነርሱ ዝግጅት ያላቸውን ያህል እንደሚሮጡት ካለፈ በኋላ ያስተላለፉት መልዕክት ጊዜውን ጠብቆ ደግሞ ከስፍራው እንዲነሳ ባለማድረጋቸው ነው የሚወቀሱት፡፡
ስለ ባለሙያዎቹ ካነሳንማ አሁን አሁን አንዳንዶቹ ጋዜጠኛን አማራሪ ሆነዋል፡፡ በአንድ ወቅት የቢሮ ፀሐፊዎች ነበሩ የሚታሙት፡፡ የሥራ ኃላፊው በቢሮቸው ሆነው ስለ አለቆቻቸው ሲጠየቁ በተደጋጋሚ «ወጣ ብለዋል» ነበር መልሳቸው፡፡ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎቹ ደግሞ ባለሙያ እንዲያገናኙ ሲጠየቁ እሺም እምቢም የሚል መልስ የላቸውም፡፡ ደርሶ ሥራ ብዙ ይሆኑና ስልካቸውንም አያነሱም፡፡ በተለይ መጀመሪያ በስልክ ከተነጋገሩ በኋላ ዳግም ሲደውሉ ስልኩ አይነሳም፡፡ እነርሱ ጠርተው ሥራቸውን ማስተዋወቅ ሲገባቸው፡፡ ምን እየሠራችሁ ነው? ሲባሉ መሸሻቸው አይገርምም?
እንዳልኳችሁ ሰሚ የሌለው መልዕክት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ መልዕከቱ ሰው ልብ ውስጥ ገብቶ የሚፈለገውን ውጤት ካላመጣ መልዕከቱ ተላልፏል ለማለት አያስደፍርም፡፡ በፌዴራል የመንግሥት ተቋማት ወይም አስፈፃሚ በሚባሉት አንድ የተለመደች አባባል አለች፡፡ ችግር ተፈጥሮ ለጥያቄ ወደ እነርሱ ሲኬድ «እኛ እኮ ሥራችን ድጋፍና ክትትል ማድረግ ነው» የሚል፡፡ ድጋፍና ክትትሉ ግንዛቤ መፍጠር፣ የአቅም ግንባታ መስጠት የተለመዱ ምላሾች፡፡ ድጋፍና ክትትላቸው በአሰራር ላይ ለውጥ ካላመጣ አሰራር አይለወጥም? ግን የአፍሪካ የህፃናት ቀን ወይም የውሃ ቀን ብቻ ሲመጣ አዘጋጆቹ እነርሱ ናቸው፡፡ መሪ ቃል እየተባለ በተለያዩ የመልዕክት ማስተላለፊያዎች ለህዝቡ የሚበተኑትን ስናይ እነዚህ ሰዎች ቀን ጠብቀው ነውን የሚመጡት? ያስብላል፡፡
ለነገሩ «አካባቢያችንን ጽዱና አረንጓዴ እናድርግ» ተብሎ የተጀመረው የአካባቢ ጽዳትስ በሁሉም ነዋሪ እኩል የሆነ ተቀባይነት መች አገኘ?፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ጽዳት ከተጀመረ ሶስተኛ ወር ቢመጣም መች በየመንደሩ ዘለቀ፡፡ እኔ የምሰጋው ታዋቂ ግለሰቦች፣ መሪዎች እየተባለ ለመጥረጊያ ግዥ የሚወጣው ወጪ የጽዳትና ውበት በጀቱን እንዳያሽቆለቁለው፡፡ አካባቢዎችም መጥረጊያ ካልተገዛልን እንዳይሉ፡፡ እዚህ ላይም መልዕክቱ የሚተላለፍበት መንገድ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
በዚህ የፅዳት ጉዳይ ላይ አዲስ አበባ ከተማ ላይ የሚስተዋለው ነገር ከተማዋ ሁለት አስተዳደር አላት እንድል ያስገድደኛል፡፡ በጣም በጥቂት በሚገለፁ የከተማዋ አካባቢዎች በአረንጓዴ ተሸፍነው ውበታቸው ይማርካል፡፡ በቴሌቪዥን መስኮት ሲታዩማ ያው እንደለመደብን ውጭ ሀገር ይመስላል፡፡ መቼም በእጅ የያዙት አይደል ነገሩ፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ ቆሻሻ በመንገድ ላይ ለመጣል የማይቀፈው ሰው ባማረው አረንጓዴ መስክ ውስጥ ፍቅሩን ሲኮመኩም አይ የኛ ሰው! ያስብላል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የሰው ዘር የሚኖርበት የማይመስል የቆሸሸ መንደር ሲያዩ አንዱ ከሌላው የሚማረው መልዕክቱ እንዴት ቢደርሰው ነው? ነገሩ ዞሮ ዞሮ አካባቢውን ከሚመራው ራስ አይወርድም፡፡ ጠንካራ የሆነ የክፍለ ከተማ መሪ ባለበት ጠንካራ ሥራ ይሠራል፡፡ከሌለ ደግሞ ያው የተለመደው ይሆናል፡፡ ለነገሩ መሪውስ ቢሆን ጥሩውን ወስዶ እርሱም እንደጥሩዎቹ እንዳይሆን ምን ያግደዋል? ሰሚ የሌላው መልዕክት እንበለው ይሆን?

ለምለም መንግሥቱ 

Published in መዝናኛ

የእረፍት ቀናትን ብዙ ለተዘዋወረባቸው ሰዎች ብዙ ያስቃኛሉ፡፡ እኔ እንኳን የእረፍት ቀኔን የማሳልፈው በመዞር ስለሆነ በሳምንት ምን ያህል ቀን እንደማርፍ ሳይሆን ምን ያህል ቀን እንደማላርፍ ብናገር ይሻለኛል፡፡ እናም ዙረት የለመደው እግሬ ባሳለፍነው ሳምንት አንድ የደረቅ ወረዳ ተብሎ የተሰየመ ሠርግ ላይ ጣለኝ፡፡ ለመታደም ከባለቤትዎ ጋር ተብሎ በተሰጠኝ የጥሪ ወረቀት መሰረት ብቻዬን ሁለት ሰው መስዬ ግር ብዬ ሄድኩኝ፡፡ ‹‹ ማግባት በር ላይ ሳማ እንደመትከል ነው›› ስለተባልኩ ነው እስካሁን ያላገባሁት፡፡
ለሠርግ የተጠራ ሳይሆን ለጦርነት እንደተጠራ ሰው ለምሳ ግብዣ ምሳዬን ግጥም አድርጌ ተመገብኩና ሄድኩ፡፡ (ስንቅ መቋጠር ብቻ ነው የቀረኝ) ይህን ያደረግኩት መብላቷን ሳታውቅ እጇን ታጠበች አይነት እንዳይሆንብኝ በማለት ሰግቼ ነው፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ሠርጎች ድግስ መስለው ድግስ ቅብ የሆኑ አሉና ነው፡፡
እንግዲህ የትዝብቴ ትኩረት ሠርጉ ላይ ሳይሆን ሙሽሪትና ሙሽራው ተያይዘው ወደ ቤታቸው ካመሩ በኋላ ማታ ላይ ለሙሽሪት የዳቦ ስም ለማውጣት የሚደረገው የስም መዋጮና የአስመራጩ ጊዜያዊ ምርጫ ቦርድ ግርግሩ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሰው ከተወለደ ጀምሮ እስከሚሞት ድረስ ቢያንስ ሦስት ስም ይኖረዋል፡፡ ለምሳሌ ቅጣው የሚባል ሰው የመጀመሪያ ስሙ አራስ( ሲወለድ የተሰጠው)፣ ዋና ስሙ ራሱ ቅጣው፣ ሲሞት የሚወጣለት ደግሞ እሬሳ ወይም አስክሬን ነው፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ ሞቶ ማየት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ስሙ እጅጉ የሆነ ሰው አይበለውና ቢሞት እጅጉ መጣ ሳይሆን ሬሳው ወይም አስክሬኑ መጣ አይደል የሚባለው፡፡ ስለዚህ የክርስትና ስም፣ ቅጽል ስም፣ የሰፈር ስም፣ ወዘተ… ሳይጨምር በትንሹ ሦስት ስሞች ይኖሩናል ማለት ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያውያንን ስሞች ስንመለከት አብዛኞቹ ከኢትዮጵያዊ ማንነቶች የራቁ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ሲደመጡ ለጆሮ እንዲጣፍጡ ተደርገው የተጋገሩ እንጂ ትርጉማቸውና ታሪካዊ አመጣጣቸው ከወዴት እንደሆነ ማወቅ ከባድ ነው፡፡ ‹‹ ወደ ትውልድ አካባቢ የሚወስደውን መንገድ በግራ እጅህ አትጠቁም›› የሚለው ተረት የሚያመለክተው የሥነ ምግባር ህግን ነው፡፡ በሌላ አነጋገር አንድ ሰው ያለበትን አካባቢ ጨምሮ ያለውን ነገር በአድናቆት መመልከትና ትውፊታዊ ስሞችንም መጠቀም እንዳለበት ለማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡
በእርግጥ አሁን ላይ ስሞች የሰው ይሁኑ የአውሬ መለየት እስኪያቅት በገፍ ይመረታሉ፡፡የጥንት ኢትዮጵያውያን የመጠሪያ ስሞችና የሠርግ የዳቦ ስሞች ግን አገራዊ ማንነትን ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ስለዚህም ከነ ሊሊ፣ ቲቲ፣ኪኪ፣ጄሪ፤ ሜሪ፣ ፊፊ፣ ወዘተ... እና መሰል አመጣጣቸው ከየት እንደሆነ የማይታወቁ አሰቃቂ ስሞች ራስን መጠበቅ ይገባል፡፡
እኔ እኮ የሀሳብ ልጓም ካላበጁልኝ ማቆሚያ የለኝም፡፡ ወደ ጉዳዬ ልመለስ፤ እናም ከሠርጉ መልስ ማታ ላይ የዳቦ ስም ለሙሽሪት ሲወጣ ቃለ ጉባኤ ያዥ ተብዬ በመመረጤ አበል ቢጤ አገኝ ብዬ በቀጥታ ወደ ሙሽሮቹ ቤት አመራሁ፡፡
በነገራችን ላይ በዳቦ የሚወጣው የዳቦ ስም እድለኛ ለሆነች እንስት የሚሰጥ ተጨማሪ ስም ነው፡፡ እናም በተገኘሁበት ሠርግ ላይ በሠርጉ ውሎ ከመታደም ባሻገር በተከበረው የሚዜዎች ቋሚ ኮሚቴ አማካኝነት የዳቦ ስም አውጪ አባል የሆኑና በእጩነት የቀረቡ አካላት እዚህም እዚያም ተሰየሙ፡፡
በአብዛኛው በአገራችን ወግ መሰረት አንዲት ሴት ለአቅመ ሄዋን ከደረሰች በኋላ ስትዳር ክብረ ንጽህናዋን ጠብቃ እንደሆነ በሠርጓ እለት ማታ ላይ በሚዜዎች አስተባባሪነት የዳቦ ስም እንዲወጣላት ይደረጋል፡፡ ዳቦው የሚቀመጠው በመሶበ ወርቅ ውስጥ ሲሆን፤ ዳቦው የሴትነቷ ምሳሌ፤ መሶበወርቁ ደግሞ ፈተናዎችን አልፋ ላገባት ሰው እንድትገባ ተደርጋ ስለመቆየቷ የሚገልጽ እንደሆነ እንጀራ እናቴ ነግራኛለች፡፡
‹‹ሰው ለወዳጁ ጫጩት ያርዳል›› እንደሚባለው የዳቦ ስም ሲወጣ የቅርብ ሰዎች ነን ከሚሉ እስከ ሩቆቹ ድረስ ቢስማማም ባይስማማም ስም ለማውጣት የመሰለውን ወርወር ያደርጋል፡፡ ታዲያ የሙሽራዋን ስብዕና በማይነካ መንገድ መሆን አለበት ‹‹የምላስ ወለምታ ከእግር ወለምታ ይከፋል›› ይባል የለ፡፡ ምላስ ልጓም ካልተደረገለት ከባድ ጉዳት ከማድረሱም በላይ ከሰዎቹ ጋር ሊያቆራርጥ ይችላልና፡፡
መጨረሻው ላይ የሚጸድቀው ግን የወንዱ ቤተሰብ ያወጣው ስም ነው፡፡ ለምን ቢሉ ከእንግዲህ የእነርሱ ልጅ ሆና ስለመጣች አዲስ ስም ማግኘት አለባት ከሚል እሳቤ የመነጨ ነው፡፡
በዚህ የስም አወጣጥ ውስጥ በእጅ ብልጫ ሌላ ሰው የሰየመው ስም አብላጫውን ድምጽ ቢያገኝም ዴሞክራሲ ብሎ ነገር አይኖርም፡፡ ለምን የቤተሰቡ ስያሜ የግድ ነውና፡፡ ስሙ ሲወጣ ከስሙ በኋላ የሚቀመጠው ቅጥያ ‹‹ወርቅ›› የሚል መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ አመለ ወርቅ፣ የሸዋ ወርቅ፣ ዙሪያሽ ወርቅ፣ አንቺነሽ ወርቅ ወዘተ... የመሳሰሉት ኢትዮጵያዊ ቀለም ያላቸው ስሞች ውድድር ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል፡፡
እኔ በቃለ ጉባኤ ያዥነት በተሰየምኩት ሠርግ ላይ ግን ዳቦው በኬክ ተቀይሮ የዳቦ ስም የሚለው ቀርቶ የኬክ ስም ተባለና የሙሽሪትን የኬክ ስም ወርቅን ብቻ አስከትሎ ‹‹ተቆራጭ ወርቅ›› ተብሎ ተሰየመ፡፡ በወንዱ ቤተሰቦች ሳይሆኑ የቃና ተከታታይ ቤተ ዘመዶች፡፡ አይ ዘመን ገና ብዙ ያሳየናል፡፡
የስም ቁንጅና ለትዳር ዋስትና አይሆንም ሲባል እሰማ ነበር፡፡ በዚህ ሠርግ ላይ ግን የሚሰጡት ስሞች ልጅቷ እንድትታወስበት ሳይሆን የስሙ ዘመናዊነት ለትዳራቸው የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የተሰየመ መሰለኝ እኔ ግን ዳግም ሌላ ሠርግ ላይ ስገኝ ‹‹የዶናት ወርቅ›› የሚል ስም እንዳልሰማ እየተመኘሁ ነገሬን ቋጨሁ፡፡

 

አዲሱ ገረመው

Published in መዝናኛ

በቤታችን ወይም በአካባቢያችን የውሃ መጥፋት ችግር አነጋጋሪ ከመሆን አልፎ በመለመዱ ውሃ የሚያገኝበትን ጊዜ ነው የምንናፍቀው፡፡ ደንበኛው በሚፈልገው ጊዜ ሳይሆን አገልግሎት ሰጭው ሲያቀርብ ነው አገልግሎቱ የሚገኘው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የሚያማርረው ውሃ የሚመጣበት ሰዓት አለመታወቁ ነው፡፡ ቧንቧ በተደጋጋሚ መከፈት፣ ሌሊት ከእንቅልፍ ነቅቶ ውሃ መኖርና አለመኖሩን ማረጋገጥ አሰልቺ ሆኗል፡፡አማራጭ ባለመኖሩም በየሰዓቱ ቧንቧ እየከፈቱ መፈተሽ ግድ ነው፡፡
ወጣት ብዙነህ መርጋ «ከዚህ በኋላ ውሃ መምጣቱን ለማረጋገጥ ከእንቅልፍ በተደጋጋሚ መንቃትም ሆነ ቧንቧ እየከፈቱ መፈተሽ» ቀርቷል ይለናል፡፡ ወጣቱ በሠራው የፈጠራ ሥራም ለቤቱ በመጠቀም ፈጠራው ችግሩን እንዴት እንዳቃለለለት በተግባር ማረጋገጡንም ገልጿል፡፡ ፈጠራውንም ብዙነህስ ቴክኖሎጂ ወይም /ቡዝቴክ/ ብሎ ሰይሞታል፡፡
ወጣቱ ሌላም የፈጠራ ሥራ አለው፡፡ የቤቱ ቁልፍ የጠፋበት ወይም ሳይጠፋበት በመቆጣጠሪያ መክፈት ለሚፈልግ ሰው የሚገለገልበት የፈጠራ ሥራ ሠርቷል፡፡ ሁለቱም የፈጠራ ሥራዎቹ በእጃችን በምንጠቀምበት ተንቀሳቃሽ ስልክ ነው የሚሠራው፡፡ ስለሁለቱም የፈጠራ ሥራዎቹና የወደፊት እቅዱ ከወጣቱ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡
ወጣት ብዙነህ ስለ ቡዝቴክ ቴክኖሎጂ ወይም የፈጠራ ሥራው እንደገለፀው ፈጠራውን የሠራው የውሃ መጥፋት የብዙ ሰዎች ችግር እና ቅሬታም በመሆኑ ነው፡፡ የሠራው የፈጠራ ሥራም ሰዎች በተንቀሳቃሽ ስልካቸው በቀላሉ በመጠቀም ችግራቸውን ለመፍታት የሚያስችላቸው ሲሆን፣ ጠፍቶ የቆየ ውሃ ሲመጣ በጥሪ ወይም በጽሁፍ መልዕክት ያሳውቃቸዋል፡፡ ሲደወል ካልተሰማ በአማራጭ ደግሞ በጽሁፍ መልዕክት መረጃው ይደርሳል፡፡ መልዕክቱ በድምፅ የታገዘ በመሆኑ አገልግሎት ፈላጊው ከሁለት በአንዱ መልዕክቱ ይደርሰዋል፡፡የቡዝቴክ አገልግሎት መቆጣጠሪያ መሣሪያ ያለውና በሲም ካርድ የሚሰራ ሲሆን፤ መረጃ የሚሰጠው ፕሮግራም ውሃ መምጣቱን እንዲያሳውቅ የሚያስችል በመሆኑ የታዘዘውን ይፈጽማል፡፡ በአካባቢው የሚገኙ ደንበኞች ሊጠቀሙበት እንዲችሉም በአንድ የመረጃ ቋት በአካባቢው 15 ለሚሆኑ ሰዎች መረጃው እንዲደርሳቸው ማድረግ ይቻላል፡፡ የተመዘገቡት ሁሉም በተመሳሳይ ሰዓት በአንድ ጊዜ መረጃው ይደርሳቸዋል፡፡ በዚህ መልኩ በየአካባቢው ለ15አባወራዎች አገልግሎትና መረጃ የሚሰጥ ፈጠራ ማዳረስ ይቻላል፡፡
የፈጠራ ሥራው የውሃ መጥፋት ችግርን ታሳቢ አደረገ እንጂ የእሳት አደጋ ሲነሳም እንዲያሳውቅ ማድረግ ይቻላል፡፡ የፈጠራ ባለሙያው ፈጠራውን መጀመሪያ የሞከረው በቴሌቪዥን መቆጣጠሪያ ወይም ሪሞት ነበር፡፡ በማሻሻል በተንቀሳቃሽ ስልክ ሠርቶ አገልግሎቱን ቀላል አድርጎታል፡፡ በአሁኑ ጊዜም 16ያህል ፕሮግራሞች ጭኗል፡፡ ወይም መረጃዎችን ማስተላለፍ እንዲችል አድርጎ አገልግሎቱን አሳድጓል፡፡ ሰው በሌለበት የቤት መስኮት ወይም በር ቢሰበር እና ሌላም ችግር ቢፈጠር መረጃው ለባለቤቱ በስልኩ ላይ በአጭር የጽሁፍ መልዕክት በቀላሉ ይደርሰዋል፡፡
ወጣቱ በውሃ አገልግሎት ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ የሠራው የፈጠራ ሥራ አንድ ነገር አስታወሰኝ፡፡በጋራ መኖሪያ ቤት ቧንቧ ከፍቶ ቤት ዘግቶ መሄድ በተደጋጋሚ ያጋጥማል፡፡ ውሃው በሚመጣበት ጊዜ የሚዘጋ ሰው ባለመኖሩ ቤት ውስጥ ሞልቶ ችግሩ ታች ለሚኖረው ሰውም እየተረፈ የብዙ ሰዎች ቤት በውሃ ተበላሽቷል፡፡ ከጎረቤት ጋር ያለመግባባት ችግርም እየፈጠረ ነው፡፡ የወጣቱ ፈጠራ እንዲህ ያለውን ችግርም ለማቃለል ይረዳል፡፡
ስለ ሌላው የፈጠራ ሥራው ወጣት ብዙነህ እንዳስረዳው የቤት በር መክፈቻና መዝጊያ የሆነውን ቁልፍ ሙሉ ለሙሉ የሚያስቀር ነው፡፡ «በኤሌክትሪክ ሲስተም» ወይም ኤሌክትሪክ በመጠቀም የቤቱን በር መክፈትና መዝጋት የሚቻልበት ዘዴ ሲሆን፣ ይህ መሣሪያ አስር በአስር ሣንቲ ሜትር በሆነ ሳጥን ውስጥ የሚቀመጥ መቆጣጠሪያ ነው፡፡ መሣሪያውንና ተንቀሳቃሽ ስልክ በማገናኘት በማንኛውም ቦታ ሆኖ በስልክ ላይ በሚላክ አጭር የጽሁፍ መልዕክት የመኖሪያ ቤት በር መዝጋትና መክፈት ይቻላል፡፡ በሩ ሲነካም መልዕክቱ በስልክ ስለሚደርስ ፈጥኖ በቦታው በመድረስ ችግሩን ለማወቅ ያስችላል፡፡
የስልካችን ባትሪ አልቆ ቢዘጋ ወይም በተለያየ ምክንያት ስልካችን በእጃችን ባይኖር ለዚህ መላ አለው፡፡የቤቱ በር ላይ የምስጢር ቁጥር ወይም ፓስወርድ በመግጠም ችግሩን መፍታት ይቻላል፡፡ በሌላ ሰው ስልክ ላይ የምስጢር ቁጥሩን በመጠቀም በሩን መክፈት ይቻላል፡፡
ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ በእጅ በማጨብጨብና በቃላት ወይም «ብራ! ጥፋ!» በማለት መብራት እንዲበራና እንዲጠፋ የሠራው የፈጠራ ሥራ ደግሞ ሌላው የፈጠራ ውጤቱ ነው፡፡ ከሠራቸው የፈጠራ ሥራዎች እነዚህ ጥቂቶቹ ሲሆኑ፤ ሌሎችም ከ40በላይ የፈጠራ ሥራዎች አሉት፡፡
የወጣቱ የፈጠራ ሥራዎች ችግር ፈች ሆነው ግን ተጠቃሚው ጋ አልደረሱም፡፡ እርሱ እንዳለው ብዙዎቹን የፈጠራ ሥራዎቹን የሠራው በትምህርት ላይ ሆኖ ነው፡፡ ወደገበያው ለመግባት ጊዜው ስላልነበረው ተጠቃሚው ጋ አላደረሳቸውም፡፡ ይህ አንዱ ምክንያት ቢሆንም በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ጥርጣሬ ደግሞ ወደ ገበያው ደፍሮ እንዲገባ አላስቻለውም፡፡ ህብረተሰቡ በሀገሩ ልጅ የፈጠራ ሥራ ላይ እምነት የለውም፡፡ ትኩረቱ የውጭ ምርት ላይ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን ወጣት ብዙነህ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች ተጋፍጦ ፈጠራዎቹ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲውሉ ማድረጉ እንደማይቀር ይገልፃል፡፡ እርሱ በተግባር ያየውን ችግር ብቻ ከመፍታት፡፡ ህብረተሰቡንም በማዳመጥና የሚፈልጉትን መነሻ በማድረግ ፈጠራውን ለመሥራት ማሰቡንም ባለሙያው ያስረዳል፡፡
ወጣት ብዙነህ በፈጠራ ሥራው 15 በሚሆኑ ውድድሮች ላይ ተሳትፏል፡፡ በከተማና በሀገር አቀፍ በተካሄዱ ከ20 በላይ በሚሆኑ ኤግዚቢሽኖች ላይ የፈጠራ ሥራዎቹን አስተዋውቋል፡፡ «ኤሌክትሪካል ሲስተም ላይ አሪፍ ዲዛይነር ነኝ» ሲልም ይገልፃል፡፡ በዘርፉ የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችለውን አቅም መፍጠሩንም ይናገራል፡፡ በአሁኑ ጊዜም በሙያው በአንድ ድርጅት ውስጥ በቅጥርና በግሉ እየሠራ መሆኑን ገልጿል፡፡
ወጣት ብዙነህ በፈጠራ ሥራው ሁለት ጊዜ የወርቅ፣ አንድ ጊዜ ደግሞ የብር ሜዳሊያ ተሸልሟል፡፡ሽልማቱንም ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደተቀበለ፤ በተለያየ ጊዜ በተዘጋጁ የቴክኖሎጂ ውድድሮች ላይ አራት ጊዜ አንደኛ ሆኖ የምስክር ወረቀቶችን ማግኘቱን፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ እውቅና የተሰጣቸው የፈጠራ ሥራዎችም እንዳሉት፤ የፈጠራ ሥራዎቹንም በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ፅህፈት ቤት ማስመዝገቡን ያብራራል፡፡
ወጣት ብዙነህ የፈጠራ ሥራው የውጭ ሀገር ነፃ የትምህርት ዕድል አስገኝቶለታል፡፡ ከውሃ አገልገሎት ጋር በተያያዘ የሚያጋጥመውን ችግር ለመፍታት በሠራው የፈጠራ ሥራ ነው ነፃ የትምህርት ዕድሉን ያገኘው፡፡ስለትምህርት ዕድሉ እንደነገረኝ ከመላው ኢትዮጵያ አንደኛ በመውጣት ነው ዕድሉን ያገኘው፡፡ ነፃ የትምህርት ዕድሉ የተሰጠው በቻይና ሀገር ሲሆን፣ የአጭር ጊዜ የኤሌክትሮኒክስ ቴክኖሎጂ ትምህርት ተምሯል፡፡ ከነፃ የትምህርት ዕድሉ ጎን ለጎን ለፈጠራ ሥራው ከነሙሉ ክብሩ የሚል የምስክር ወረቀት አግኝቷል፡፡
የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ይህን ዕድል ሲሰጠው ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶታል፡፡ ሽልማቱም የትምህርት ዕድሉም የበለጠ እንዲሠራ ያስቻለው መሆኑንም ገልጿል፡፡
በቻይና የአጭር ጊዜ ቆይታው ከትምህርቱ ጎን ለጎን በፈጠራ ሥራ ኢትዮጵያ የምትገኝበትንና ሌላው ዓለም የት እንደደረሰ ጥሩ ግንዛቤ ያገኘበት እንደነበርም አስታውሷል፡፡ በትምህርት ቆይታው «የቻይናውያኑ መልካም የሆነ አስተሳሰብ በኢትዮጵያም ቢኖር» ብሎ በሀገሪቱ ዜጎች ያየው በጎነት መንፈሳዊ ቅናት አሳድሮበታል፡፡ እርሱ እንዳለው የሀገሪቷ ዜጎች ለፈጠራ ባለሙያው ክብርና ከፍተኛ ዋጋ ይሰጣሉ፡፡ የሀገሩ መንግሥትም ለዜጎቹ የፈጠራ ባለሙያዎች ቅድሚያ በመስጠትና የሚያስፈልጋቸውን በማሟላት የሚያደርገው ድጋፍም አስደስቶታል፡፡ ትልቅ ዋጋ እንዳለውም ያምናል፡፡ የፈጠራ ባለሙያዎቹን ቅንነትም አድንቋል፡፡ ወጣት ብዙነህ ከራሱ አልፎ ለዜጎች የሥራ እድል የሚፈጥር የፈጠራ ሥራ ለመሥራት ማቀዱን በነበረን ቆይታ ገልጾልኛል፡፡ ውጤታማ ባለሙያ እንዲሆን እንመኝለታለን፡፡ ባለፈው ሳምንት የወጣቱን ሌሎች የፈጠራ ሥራዎች ማስነበባችን ይታወሳል፡፡

ለምለም ምንግሥቱ 

Published in ማህበራዊ

አመልካች፡-አቶ እንዳይላሉ ተገኝ
ተጠሪ፡- አቶ መሸሻ ዘመዴ
ጉዳዩ የዋስትና መብት ይከበርልኝ ጥያቄን የሚመለከት ሲሆን፤ ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ በአመልካችና በሌሎች ሦስት ግለሰቦች ላይ በመሰረተው የወንጀል ክስ ነው፡፡ ክሱ በፍርድ ቤት መታየት ከቀጠለ በኋላም አመልካች የተከሰሰበት የወንጀል ጉዳይ የዋስትና መብት የማይከለክል በመሆኑ የዋስትና መብታቸው ተከብሮላቸው ቆይቷል፡፡ ከዚህ በኋላም ዓቃቤ ሕግ የተፈቀደውን የዋስትና መብት ሊያስነሳ የሚችል አዲስ ነገር መገኘቱን ገልጾ፤ ለአመልካች የተከበረላቸው የዋስትና መብት በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 74 መሰረት እንዲነሳ አመልክቷል፡፡
ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ ሲመለከት የነበረው የፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም ጉዳዩን ተመልክቶ ለአመልካች የተከበረላቸውን የዋስትና መብት የሚያስነሳ ፍሬ ነገር ተገኝቷል የሚል ምክንያት በመያዝ ቀድሞ የሰጠውን ትዕዛዝ በመቀየር የአመልካችንና የሌሎችን ተከሳሾች የዋስትና መብት ነፍጓል፡፡ ከዚህም በኋላ አመልካችና ሌሎች አብሯቸው የተከሰሱና የዋስትና መብት በማክበር የተሰጠው ትዕዛዝ የተነሳባቸው ሰዎች ይግባኛቸውን ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ግራ ቀኙን ከተከራከሩ በኋላ የስር ፍርድ ቤት በድጋሚ የሰጠው ትዕዛዝ ተሽሮ የዋስትና መብት ተከብሮላቸዋል፡፡ ከዚህም በኋላ አቃቤ ሕግ አመልካችና ሌሎች አብሯቸው የተከሰሱ ሰዎች የዐቃቤ ሕግ ምስክር የሆነውን ሰው ሌላ ሰው ልከው አስፈራርተዋል፤ የዋስትና መብት በማክበር የሰጠው ትዕዛዝ በ/ወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 74 መሠረት ተነስቶ ጉዳያቸውን ማረሚያ ቤት ሁነው እንዲከታተሉ ሲል ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታውን አቅርቧል፡፡
ፍርድ ቤቱም አስፈራርተውታል የተባለውን የዓቃቤ ሕግ ምስክር በችሎት አስቀርቦ በመስማትና ምስክሩ በጉዳዩ ላይ በተከሰሱ ሰዎች ማስፈራራት እንደተፈፀመበት መመስከሩን በማረጋገጥ ቀድሞ የአመልካችን የዋስትና መብት በማክበር የሰጠውን ትዕዛዝ በማንሳት ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ሲል ወስኗል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡
የአመልካች ጠበቃ ነሐሴ 20 ቀን 2002 ዓ.ም በጻፉት ሁለት ገፅ የሰበር አቤቱታ በጉዳዩ ላይ በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል የሚሉበትን ምክንያት ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ፡- አስፈራርተውታል የተባለው የአቃቤ ሕግ ምስክር አመልካች በላኩት ሰው ያስፈራሩት ስለመሆኑ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ የዋስትና መብቱ መነሳቱ ያላግባብ ስለሆነ ሊታረም የሚገባው ነው በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም በሰበር ችሎቱ ሊታይ የሚገባው ነው ተብሎ በመታመኑ ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎለት መልሱን ሰጥቷል፡፡ በመልሱም ላይ የአመልካች የሰበር አቤቱታ የቀረበው ሥነ-ሥርዓቱን ጠብቆ ያለመሆኑንና የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው ትዕዛዝ በማስረጃ በተረጋገጠ ፍሬ ነገር ላይ የመሰረተ መሆኑን ገልጾ የአመልካች አቤቱታ ውድቅ እንዲሆን ተከራክሯል፡፡ የአመልካች ጠበቃ በበኩላቸው አስፈራርተውታል የተባለው የዓቃቤ ሕግ ምስክር በዋናው ጉዳይ ላይ የምስክርነት ቃሉን ሰጥቶ ያበቃ መሆኑን በመጨመር የሰበር አቤቱታቸውን አጠናክረው ተከራክረዋል፡፡
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለ መልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን፤ ይህ ሰበር ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው የሕግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡
የአመልካች የሰበር አቤቱታ ሥነ ሥርዓቱን ጨርሶ የቀረበ መሆን ያለመሆኑን በመመልከት የአመልካች የዋስትና መብት መጀመሪያ በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከተሰጠ በኋላ አዲስ ነገር ተገኝቷል በሚል ምክንያት በአቃቤ ሕግ አቤቱታ አቅራቢነት በስር ፍርድ ቤት ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን በዚህ ትዕዛዝ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው የስር ፍርድ ቤት የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ ቁጥር 74 ድንጋጌን መሰረት በማድረግ የሰጠውን ትዕዛዝ የተሻረ ቢሆንም አቃቤ ህጉ ለዚሁ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት አዲስ ነገር ተገኝቷል በሚል በድጋሚ የአመልካች የዋስትና መብት እንዲነሳ አመልክቷል፡፡ ፍርድ ቤቱም ምስክር ሰምቶ በአቃቤ ሕግ በኩል የተገለጸው ፍሬ ጉዳይ በማስረጃ መረጋገጡን በመያዝ የአመልካችን የዋስትና መብት በማክበር የሰጠውን ትዕዛዝ አንስቶታል፡፡ ከዚህ መገንዘብ የሚቻለው በውጤት ደረጃ ሁለቱም የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት ትዕዛዝ ተመሳሳይ መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም ጉዳዩ በሰበር ችሎቱ መቅረቡ ሥነ ሥርዓቱን ሳይጠብቅ ነው ለማለት የሚያስችል ባለመሆኑ በዚህ ረገድ ተጠሪ ያቀረበው ክርክር ተቀባይነት ያለው ሆኖ አልተገኘም፡፡
አመልካች የተከሰሱበት የወንጀል ድርጊት የዋስትና መብት የማይከለክል ሲሆን የዋስትና መብታቸው ከተከበረላቸው በኋላ ሊከለከል የቻለው የዓቃቤ ሕግ ምስክርን በሌላ ሰው አስፈራርተዋል በሚል ምክንያት ነው፡፡ ዋስትና የተፈቀደለት ሰው በዋስ ከወጣ በኋላ አዲስ ነገር ከተገኘ ፍርድ ቤቱ በማናቸውም ጊዜ ቢሆን በስልጣኑ ወይም በማናቸውም ባለጉዳይ አመልካችነት በዋስትና ወረቀት የተለቀቀው ሰው የተለቀቀበትን ሁኔታዎች (ግዴታዎች) እንደገና ተመልክቶ የተለቀቀው ሰው አዲስ ዋሶችን እንዲያመጣ ወይም በማረፊያ ቤት እንዲቆይ ለማዘዝ የሚቻል ስለመሆኑ የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ ቁጥር 74 ድንጋጌ በግልፅ ያሳያል፡፡
የአመልካችን የዋስትና መብት በማክበር ተግባር ፈፅመዋል በሚል ምክንያት፤ ምስክሩን አስፈራርተውት ስለመሆኑ ደግሞ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አረጋግጧል። በዚህ ረገድ የአመልካች ጠበቃ አጥብቀው የሚከራከሩት ምስክሩ በአመልካች በቀጥታ ወይም አመልካች ራሳቸው በላኩት ሰው እንዳስፈራሩት አልተረጋገጠም በሚል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይኽው የአመልካች ጠበቃ ክርክር የፍሬ ነገር ክርክር ሲሆን፤ ፍሬ ነገርን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ሥልጣን ያለው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያረጋገጠው ደግሞ ይህ ሰበር ችሎት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕግ መንግሥት አንቀጽ 80(3)(ሀ)) እና በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 መሰረት የተሰጠው ሥልጣን ፍሬ ነገርን የማጣራት ወይም ማስረጃን መመዘን ባለመሆኑ በዚህ ችሎታ ሊታይ የሚገባው አይደለም፡፡ በመሆኑም በዚህ ረገድ የአመልካች ጠበቃ ያቀረቡትን ክርክር አልተቀበልነውም፡፡ በዚህም መሠረት የአቃቤ ሕግ ምስክር እንዳስፈራሩት ከተረጋገጠ ምክንያቱ እንደአዲስ ነገር መገኘት የሚታይ ሲሆን፤ የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ ቁጥር 67(ለ) እና (ሐ) ድንጋጌዎች መንፈስ ጋር ተዳምሮ ሲታይ ለአመልካች የተከበረውን የዋስትና መብት እንደገና ለማንሳት የሚያስችል ሕጋዊ ምክንያት ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ ረገድ በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ትዕዛዝ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያሉት ነው ለማለት የሚያስችል ምክንያት የለም፡፡
ሌላው የአመልካች ጠበቃ በዚህ ችሎት በመልስ መልሳቸው ላይ ያነሱት ክርክር አስፈራርተውታል የተባለው ምስክር በጉዳዩ ላይ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተው ጉዳዩ አብቅቷል የሚለው ሲሆን፤ ይህ ነጥብ በዚህ ችሎት የተነሳ አዲስ ነጥብ ሲሆን፤ ችሎቱ መመርመር ያለበት የስር ፍርድ ቤቶችን የውሳኔ ግልባጭ መሠረት በማድረግ በሕግ አተረጓጎም ወይም አተገባበር ረገድ የፈፀመ መሰረታዊ የሕግ ስህተት አለበት ለማለት የሚያስችል የክርክር ነጥብ አይደለም፡፡ የአመልካች ጠበቃ አስፈራርተውታል የተባለው ምስክር በጉዳዩ ላይ መስክሮ ጉዳዩ አብቅቷል የሚሉ ከሆነም አዲስ ነገር መገኘቱን መሠረት በማድረግ የዋስትና መብቱን ለከለከለው ፍርድ ቤት ጥያቄአቸውን ከሚያቀርቡና በሚሰጠው ትዕዛዝም ቅሬታ ካላቸውም ተዋዕረዱን ጠብቀው የይግባኝ ቅሬታቸውን ወይም የሰበር አቤቱታቸውን ከሚያቀርቡ በስተቀር በዚህ ችሎት ጉዳዩን ለማየት የሚያስችል ሆኖ አልተገኘም፡፡ በአጠቃላይ ከላይ በተመለከቱት ምክንያቶች በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ትዕዛዝ መሠረዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ነው ለማለት ስላልተቻለ ተከታዩ ተወስኗል፡፡
ውሳኔ
1. በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ትዕዛዝ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ ቁጥር 72(2) መሰረት ፀንቷል፡፡
2. መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

አያሌው ንጉሤ

Published in ፖለቲካ

ኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግብን እና የድህነት ቅነሳ ፕሮግራምን ለማሳካት ከያዘቻቸው መርሐ ግብሮች መካከል አንዱ አስተማማኝነት ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ለዜጎች ማዳረስ ነው፡፡ ይህን እውን ለማድረግና ለማሳካትም የአገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም በ1998 ዓ.ም ይፋ ተደርጎ በፕሮግራሙ የአገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል ሽፋንና አቅርቦት የሚያሳድጉ ልዩ ልዩ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡
የአገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም ለገጠር ከተሞች፣ ቀበሌዎችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎትን በማዳረስ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ሽፋንን የማሳደግ እንዲሁም የቀበሌዎችና መንደሮችን የመልሶ ግንባታ ሥራን በማከናወን የኤሌክትሪክ አቅርቦት አስተማማኝነትን የመጨመርና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የመፍታት ዋና ዋና ዓላማዎች አሉት፡፡
ከ2002 ዓ.ም እስከ 2007 ዓ.ም በተተ ገበረው የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መጨረሻ ላይ 4727 ከተሞች በአገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም ተጠቃሚ የሆኑ ሲሆን፣ የኤሌክትሪክ ሽፋኑም 54 ነጥብ 25 በመቶ ደርሷል፡፡
ይህንን የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ሽፋን እውን ለማድረግም ከመካከለኛ እና ዝቅተኛ መስመር ግንባታ በተጨማሪ 1ሺ 513 ኪሎ ሜትር የሚሆን የማስተላለፊያ መስመር እንዲሁም የ65 የማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ እና ማስፋፊያ ሥራ ተከናውኗል፡፡
በርካታ መሰናክሎችን የማለፍ ግዴታ ቢኖርባቸውም የኤሌክትሪክ ፖል በማምረትና በኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ላይ የተሰማሩ ማኅበራትና ኢንተርፕራይዞች ደግሞ በዚህ ሂደት ውስጥ ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ይነገራል፡፡ እነዚህ ማኅበራት ተደራጅተው ወደ ሥራ እንዲገቡ በመደረጉ በአገሪቱ የነበረውን የአነስተኛ ቮልቴጅ ተሸካሚ የኮንክሪት ፖል አቅርቦት እንዲሁም የመስመር ዝርጋታን ለማከናወን ተቋራጭ በማፈላለግ የሚፈጠሩ ችግሮችን መፍታትና በዚህ ዘርፍም በርካታ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር እንደተቻለ ይገልፃሉ፡፡
በኦሮሚያ ክልል ወሊሶ ከተማ በኮንክሪት ፖል ማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ በጋሻው ልመንህ እንደሚናገሩት፣ የተሰማሩበት የሥራ መስክ አዋጭና ጥሩ ነው፡፡ ‹‹ከሥራ አጥነት አውጥቶናል፡፡ በሥራችንም ተሸላሚ ሆነን ወደ መካከለኛ ባለሀብትነት ለመሸጋገር ችለናል›› ይላሉ፡፡ ሥራው ውጤት ቢያስገኝላቸውም ከችግር የፃዳ እንዳልሆነም ያስረዳሉ፡፡
ሚኒስቴሩ ለማኅበራቱ የሚያደርገው ድጋፍ ጥሩ ቢሆንም በታችኞቹ የአስተዳደር እርከኖች ላይ (በከተሞች) ስለጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራት የሚስተዋሉ የአመለካከት ችግሮች እንዳሉና ይህ የአመለካከት ችግርም ለማኅበራቱ በሚደረጉ ድጋፎችና ክትትሎች ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እያስከተለ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡
‹‹በአሁኑ ወቅት የኮንክሪት ፖል ሥራ ይቆማል የሚባል መረጃ አለ፡፡ ማኅበራችን ደግሞ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ንብረት አለው›› በማለት ስጋታቸውን ይናገራሉ፡፡ አቶ በጋሻው እንደሚሉት፣ ማኅበራቸው ወደ ኢንዱስትሪና ማኑፋክቸሪንግ ለመሸጋገር የአዋጭነት ጥናት ሰርተንና ረቂቅ አዘጋጅቶ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር ግንኙነት መፍጠር ጀምሮ ነበር፡፡ መሬት ለማኅበራት ማሸጋገር ያለመቻልና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች በክልል ከተሞች ዘንድ በመስተዋላቸው በሥራቸው ላይ ጫና እንዳሳደረባቸው በመግለፅ መንግሥት ምላሽ እንደሚሰጣቸው ያላቸውን ተስፋ ይገልፃሉ፡፡
አቶ ያሲን መሐመድ በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ጂግጂጋ ከተማ በኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ስራ የተሰማራ ማኅበር አባል ናቸው፡፡ እንደ እርሳቸው ገለፃ፣ ማኅበሩ የተመሰረተው በ2006 ዓ.ም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ከቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋማት በተመረቁ 13 የኤሌክትሪክ፣ የሲቪል፣ የመካኒካል መሃንዲሶችና ባለሙያዎች ነው፡፡ የሥራቸው ዋና ትኩረትም መብራት ያልደረሰባቸው ከተሞችና ቀበሌዎች ላይ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ሥራ ማከናወን ነው፡፡
በሥራው ላይ ከተሰማሩ ወዲህ ብዙ ጥቅሞችን ማግኘታቸውን የሚናገሩት አቶ ያሲን፣ በሥራው ሂደት ላይ ችግሮች እንዳጋጠሟቸውም ከመግለፅ አልሸሸጉም፡፡ ‹‹ሥራውን ስንጀምር ብዙ መሰናክሎች አጋጥመውናል፤ አሁንም ችግሮች አሉ›› የሚሉት አቶ ያሲን፣ የእቃ አቅርቦት ችግር ዋናውና ተጠቃሽ መሰናክል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ፖል አምራቾች ላይ የሚስተዋሉ ጥራት ችግሮች እንዳሉም ጨምረው ይገልፃሉ፡፡ ከክፍያ ጋር በተያያዘ ግን በ2008 ዓ.ም የክፍያ መዘግየት ተስተውሎ የነበረ ቢሆንም አሁን እንደተስተካከለ ጠቁመዋል፡፡
‹‹የእቃ አቅርቦቱን ጨምሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ ብዙ መሻሻሎች እየተስተዋሉ ቢሆንም ማኅበራችን ባቀደውና በሚፈለገው መጠን እየሰራን አይደለም›› ይላሉ፡፡ በተለይም ደግሞ በእቃዎች አቅርቦትና ከውጭ በሚገቡ እቃዎች ላይ የሚስተዋሉ መጓተቶች እልባት አግኝተው የሚፈለገውን ያህል ሥራ እንዲሰሩና የታሰበው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እቅድ እንዲሳካ የመንግሥት ድጋፍ እንዲደረግላቸው ያሳስባሉ፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአገራዊ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም የፕላኒንግና ኢንጅነሪንግ ኃላፊ አቶ ጫላ አማን በማኅበራትና ኢንተርፕራይዞች በኩል የተነሱ ጥያቄዎች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ እንደእርሳቸው ማብራሪያ፣ ምላሽ ያገኙና ገና በመፈታት ሂደት ላይ ያሉና ውሳኔ የሚሹ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለአብነት ያህል የዕቃ ክፍፍል ግልጽነት፣ የማኅበራት የሥራ አሰጣጥ፣ የኮንክሪት የዋጋ ክለሳ፣ የምሰሶ ፍተሻ እና የአሮጌ መስመር ማንሳትን በተመለከተ ከማኅበራትና ኢንተርፕራይዞች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እንደተሞከረም ያስረዳሉ፡፡
የግብአት በተለይ ደግሞ የትራንስፎርመር እና ኢንሱሌተር አቅርቦት፣ የከፍተኛ መስመር ኮንክሪት ምሰሶ እጥረት፣ምርት መዘግየት፣ የከተሞችና መንደሮች የኃይል ዝርጋታ ግንባታቸው ከተጠናቀቀ በኋላ የርክክብ መዘግየት፣ የመሠረተ ልማት ያለመሟላት (ግንባታ በሚከናወንባቸው የገጠር ቀበሌዎችና መንደሮች ለግንባታ ሥራ ወደ አመቺ የሆኑ መንገዶች ያለመኖር)፣ የአንዳንድ ማህበራትና የሥራ ተቋራጮች አፈጻጸም ብቃት ማነስ፣ በክረምትና በሰብል ወቅት ግንባታ የማከናወን አስቸጋሪነት መሆኑ፣ ከፕሮግራሙ ሥራ ውጭ የሚከናወኑ ተጨማሪ ሥራዎች ያለውን የግብዓት አቅርቦት፣ የተሽከርካሪና የሰው ኃይል የመሻማት፣ የከባድ ተሽከርካሪዎች ብልሽት መብዛትና የጥገና ጊዜ መራዘም፣ የማከፋፈያ ጣቢያዎች አቅም ማነስ፣ በተገነቡ መስመሮች ላይ ኃላፊነት በጎደላቸው ግለሰቦች የሚደርስ ጉዳት እንዲሁም ከወሰን ማስከበር ሥራ ጋር የተያያዙ መሰናክሎች እንደነበሩ ያብራራሉ፡፡ ችግሮቹን ለመፍታትም ጥረት መደረጉንና እንደመፍትሄ የተያዙ አቅጣጫዎች እንዳሉ በመጠቆም፡፡
ከዚህ በተጨማሪም፣ ከተገልጋይ፣ ከፋይናንስ፣ ከውስጥ አሰራር እንዲሁም ከመማርና ዕድገት አንፃር የተያዙ እቅዶች ዋና ዋና የሚዛናዊ ውጤት ተኮር ግቦች ተደርገው ተይዘው እየተሰራ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡
እንደ አቶ ጫላ ገለፃ፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በዘርፉ የተያዘውን ግብ ለማሳካትም በአገር አቀፍ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም መጠነ ሰፊ የማስተላለፊያ መስመሮች ግንባታና ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የአዳዲስ ማከፋፈያና ማስተላለፊያ መስመሮች ግንባታ እንዲሁም የማስፋፊያ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል፡፡ እነዚህን የማስተላለፊያ መስመሮችና የማስፋፊያ ሥራዎችን በአብዛኛው በውስጥ አቅም፣ በማኅበራትና በአገር በቀል ሥራ ተቋራጮች ኮንትራክተሮች በማከናወን አገራዊ አቅምን ለማሳደግም ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
ከዚህም በተጓዳኝ በክልሎች ተመርጠው እና ቅደም ተከተል ተሰጥቷቸው ለተላኩ መንደሮችና የገጠር ቀበሌዎች የቅድመ ዲዛይን ጥናት በማከናወን የገጠር ከተሞች ዝርዝር የዲዛይን፣ የግንባታ፤ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎችን በፕሮግራሙ የሪጅን ቢሮዎች አማካኝነት በማከናወን የኃይል አቅርቦት ማስፋፋት ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡
በ2010 የበጀት ዓመት በየመጀመሪያው ግማሽ የበጀት ዓመት (እስከ ታኀሣሥ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ) 289 ቀበሌዎችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ኃይል ተገናኝቶላቸዋል፡፡ በዚህም የዕቅዱን 77 ነጥብ 69 በመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡ በዓለም ባንክና በኦፊድ (OFID) ፋይናንስ ፈንድ የሚከናወነው የአዲስ አበባ፣ ባሕር ዳር፣ መቐለ፣ ደሴ፣ ድሬዳዋ፣ አዳማ፣ ሐዋሳ እና ጅማ የስርጭት መስመር ማሻሻያና የኔትወርክ መቆጣጠሪያ ግንባታ ፕሮጀክት አጠቃላይ አፈፃፀምም 84 ነጥብ 58 በመቶ ደርሷል፡፡
10ሺ 205 የገጠር ቀበሌዎችና መንደሮች የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንዲኖራቸው በማድረግ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የዕድገት ግቦች በተለይ የድህነት ቅነሳ፣ የትምህርትና የጤና ሽፋን እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ ግቦች እንዲሣኩ አስተዋፅኦ ለማበርከትና ለመስኖ ልማት መስፋፋት የሚያስፈልገውን የኃይል አቅርቦት በማመቻቸት የግብርና ልማቱ ዘርፍ ዕድገት እንዲፋጠን ለማገዝ ታቅዶ እየተሰራም እንደሆነ ያብራራሉ፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጎሳዬ መንግሥቴ በበኩላቸው፣ ማኅበራቱ በሚያመርቱት ምርት እና ለሥራው በሚመደበው በጀት መካከል አለመጣጣም እንደሚስተዋል፤ እንዲሁም አንዳንዶቹ እቃዎች የውጭ ምንዛሪ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑና የውጭ ምንዛሪ እጥረት በሚያጋጥም ጊዜ የአቅርቦት እጥረትና መጓተት እንደሚከሰት ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች በሚተከሉበትና መስመሮች በሚዘረጉበት ወቅት የሚስተዋሉ የጥራት ችግሮችም በሕብረተሰቡ ዘንድ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እንደሚፈጥሩም ይገልፃሉ፡፡ ማኅበራቱ ያመረቷቸው የኮንክሪት ፖሎች ‹‹ብርሃን ለሁሉም›› ለተባለው አዲሱ የኤሌክትሪክ አቅርቦት መርሃ ግብር ጠቀሜታ እንደሚውሉም ዋና ሥራ አስፈፃሚው ያስረዳሉ፡፡
‹‹ማኅበራቱ ለአገሪቱ የኤሌክትሪክ አቅርቦት መሻሻልና ማደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክ ተዋል፤አገራዊ አቅምን ለማሳደግና የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማበረታታት በማሰብ ክልሎችና የፌዴራል መንግሥት ለማኅበራቱ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ›› የሚሉት አቶ ጎሳዬ፣ ማኅበራቱ አገራዊ አቅምን ከማሳደግ በተጨማሪ ለጥራትም ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ያሳስባሉ፡፡
በማኅበራት ተደራጅተው በኤሌክትሪክ ኃይል ግብዓቶች አቅርቦት ላይ የሚሰሩ አካላት የኤሌክትሪክ አቅርቦትንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ታስቦ በመተግበር ላይ ለሚገኘው የአገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም ውጤታማነት ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከቱ በመሆናቸው መንግሥት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የሚገልፁት ደግሞ በውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር የኤሌክትሪክ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍሬሕይወት ወልደሃና ናቸው፡፡ እንደሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ፣ ፕሮግራሙ በርካታ ዜጎች በተለይም በገጠሪቱ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን ተጠቃሚ በማድረጉ በአገር አቀፍ ደረጃ ለተመዘገበው የኤሌክትሪክ አቅርቦት ትልቅ ድርሻ አበርክቷል፡፡ ለመርሐ ግብሩ ስኬት ድርሻ ለነበራቸው ማኅበራት ድጋፍ ማድረግ በአገር አቀፍ ደረጃ ለታቀደው የኤሌክትሪክ አቅርቦት ምቹ ሁኔታ መፍጠር በመሆኑ ድጋፉና ክትትሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

 

አንተነህ ቸሬ

Published in ኢኮኖሚ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የደቡብ ሱዳን ተልዕኮ (UNMISS) ከ300 በላይ ሕፃናት ወታዶሮችን ከደቡብ ሱዳን አማፂያንና ከታጣቂ ቡድኖች ማስለቀቁን አስታውቋል፡፡ የድርጅቱ ተልዕኮ ካስለቀቃቸው ሕፃናት 311 መካከል 87 የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውም ተነግሯል፡፡ የተልዕኮው ኃላፊ ደቪድ ሽረር የሕፃናቱን መለቀቅ አስመልክተው ያሚቦ በተባለች ከተማ በተዘጋጀ ስነ ስርዓት ላይ፣ ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ሴት ሕፃናት ከአማፂያንና ከታጣቂ ቡድኖች ነፃ ሲወጡ ይህ የመጀመሪያው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
‹‹ሕፃናት ሕልውናቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ ሲጫወቱና ሲማሩ እንጂ የጦር መሳሪያ ይዘው እርስ በእርሳቸው ሲገዳደሉ ማየት አይገባም›› ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ ነፃ የወጡት ሕፃናት ወደ ማኅበረሰቡ ሲመለሱ መገለል እንዳይደርስ ባቸውና በአማፂያኑና በታጣቂዎቹ ቁጥጥር ስር በነበሩባቸው ጊዜያት ፆታዊ ጥቃትን ጨምሮ ብዙ በደሎች ተፈፅመውባቸው ሊሆን ስለሚችል ስነ-ልቦናዊ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የደቡብ ሱዳን ተልዕኮ ባደረገው ጥናት መሰረት የደቡብ ሱዳን ነፃነት ንቅናቄ የሚባለው ቡድን 563፣ የሱዳን ሕዝቦች ነፃነት ጦር ደግሞ 137 ሕፃናት ወታደሮችን መልምለው ለውጊያ አሰማርተዋል፡፡
እ.አ.አ በሐምሌ 2011 ከሱዳን በመገንጠል ነፃነቷን ያወጀችው ምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ደቡብ ሱዳን፣ ነፃነቷን ባወጀች ማግስት ነበር ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ የተዘፈቀችው፡፡ እ.አ.አ በታኅሳሥ 2013 የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ምክትላቸው የነበሩት ዶክተር ሪክ ማቻር “የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አድርገው ብኛል” ብለው ከስልጣን ካባረሯቸው በኋላ በሁለቱ ግለሰቦች ደጋፊዎች መካከል የተነሳው ግጭት አሁንም ድረስ አላባራም፡፡
እ.አ.አ በ2015 የሰላም ሰምምነት የተፈራረሙት ሁለቱ የአገሪቱ ኃይሎች ብዙም ሳይቆዩ ወደተለመደው ውጊያቸው ገብተው የአገሪቱን ሕዝቦች ለከፋ ድርቅና ረሃብ እንዲጋለጡ አድርዋቸዋል፡፡ በዚህም ለበሽታ፣ ለስደትና ለሞት የተዳረገው የአገሬው ሕዝብ ስፍር ቁጥር የለውም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ግንቦት ወር ከኃላፊነታቸው የተሰናበቱትና ሰሞኑን ለሕክምና ወደ ኬንያ የሄዱት የቀድሞው የአገሪቱ የጦር ኃይል አዛዥ ጀኔራል ፖል ማሎንግ ወደ ደቡብ ሱዳን እንደማይመለሱ አስታውቀዋል፡፡
እንደ ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት ሁሉ የዲንቃ ጎሳ ተወላጅ የሆኑት ጀኔራል ፖል ማሎንግ በሌሎች ጎሳ አባላት ላይ ጭፍጨፋ ፈፅመዋል የሚል ተደጋጋሚ ወቀሳ ይቀርብ ባቸዋል፡፡ ከስልጣናቸው የተሰናበቱትም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ኃይሎች ይሰነዘርባቸው በነበረው ወቀሳና ክስ ምክንያት ነው ተብሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ሰላማዊ ዜጎች የግድያ፣ የአስደገድዶ መድፈርና የሌሎች ወንጀሎች ሰላባ እንዲሆኑ ምክንያት ስለመሆናቸውም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የአፍሪካ ኅብረት ጠንከር ያሉ ወቀሳዎችን አቅርበውባቸው ነበር፡፡
ጀኔራል ፖል ማሎንግ የደቡብ ሱዳን መንግሥትና አማፂያን እ.አ.አ በ2015 የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት እንዲፈርስ ምክንያት ስለመሆናቸው በርካቶች ይስማማሉ፡፡ ከዚህ ባሻገርም እ.አ.አ በሐምሌ ወር 2017 በአገሪቱ ዋና ከተማ ጁባ ከተቀሰቀሰውና የበርካቶችን ሕይወት ከቀጠፈው ግጭት ጀርባ እንዳሉም ይነገራል፡፡
በርካታ የአገሪቱ የጦር ኃይል ባለስልጣናት የጀኔራል ፖል ማሎንግ ድርጊቶችን በመቃወም ቀደም ባሉት ጊዜያት ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸው የሚታወስ ነው፡፡ ከእነዚህ የጦር ኃይሉ ባለስልጣናት አንዱ የሆኑት ሌተናል ጀኔራል ቶማስ ሲሪሎ የራሳቸውን አማፂ ቡድን አቋቁመው የመንግሥትን ኃይሎች ለመፋለም ወስነዋል መባሉ አይዘነጋም፡፡

 

አንተነህ ቸሬ

Published in ዓለም አቀፍ

ለወራት ሲደረግ የነበረው የጀርመን ፖለቲከኞች ድርድር ጥምር መንግሥት ለመመስረት የሚያስችላቸው ስምምነት ላይ አድርሷቸዋል ተብሏል፡፡ ክርስቲያን ዴሞክራሲያዊ ኅብረት የተባለው የመራሂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ወግ አጥባቂ የፖለቲካ ማኅበርና የባቫሪያ ክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ተወካዮች፣ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ከተባለው ከዋነኛው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር ጥምር መንግሥት ለመመስረት የሚያስችል ስምምነት ላይ ደርሰዋል ተብሏል፡፡
እ.አ.አ በመስከረም 2017 በተካሄደው ምርጫ ለምርጫው ከቀረቡት ፓርቲዎች መካከል አንዱም እንኳ መንግሥት ለመመስረት የሚያስችለውን አብላጫ ድምፅ ባለማግኘቱና ዋነኞቹ የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስካሁን ድረስ ጥምር መንግሥት ለመመስረት የሚያስችል ስምምነት ላይ አለመድረሳቸው በአውሮፓዋ ኃያል አገር ፖለቲካ ላይ ጥላ አጥልቶ ቆይቷል፡፡
ፓርቲዎቹ ሰሞኑን ባደረጉት ስምምነት መሰረት እ.አ.አ ከ2005 ጀምሮ ጀርመንን እየመሩ የሚገኙት ወይዘሮ አንጌላ ሜርክል ለአራተኛ ተከታታይ ጊዜ በመራሂተ-መንግሥትነታቸው ይቀጥላሉ፡፡ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል፣ በድርድሩ ወቅት ከተፎካካሪዎቻቸው ጠንከር ያሉ የመደራደሪያ ሃሳቦች ቀርበው እንደነበርና በመጨረሻም አስተማማኝ የፋይናንስ መሰረት ያለው የተረጋጋ መንግሥት ለመመስረት ከስምምነት ላይ መደረሱን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል፡፡
የዋነኛው ተፎካካሪ ፓርቲ ማለትም የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበሩ ማርቲን ሹልዝ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደሚሆኑም ተጠቁሟል፡፡ በስምምነቱ መሰረትም ጀርመን በአውሮፓ ባላት አቋም ላይ ማስተካከያዎችንና ለውጦችን ልታደርግ እንደምትችል ሊቀ-መንበሩ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ስምምነቱን መሰረት በማድረግ ጀርመን በአውሮፓ ኅብረት ውስጥ ያላትን የመሪነት ሚና የበለጠ ታሳድጋለች፤ ለኅብረቱ በጀት የምትመድበውን የገንዘብ መጠንም ትጨምራለች›› ብለዋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት የምጣኔ ሀብት ኮሚሽነር የሆኑት ፔር ሞስኮቪቺ በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ በፓርቲዎቹ መካከል የተደረገውን ስምምነት ‹‹መልካም ዜና›› በማለት ተቀብለውታል፡፡ ስምምነቱ ለጀርመን ብቻ ሳይሆን ለአውሮፓ ኅብረትም መልካም እንደሆነ ገልፀው ተደራዳሪ ወገኖችን አመስግነዋል፡፡
የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ፖለቲከኞች የፋይናስ እንዲሁም የሰው ሀብትና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትርነትን ጨምሮ ስድስት የሚኒስትርነት ቦታዎችን እንደሚይዙ ይጠበቃል፡፡ የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ እ.አ.አ ከ2005 እስከ 2009 እንዲሁም ከ2013 እስከ 2017 በነበሩት ጥምር መንግሥታት ከመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ፓርቲ ጋር ጥምረት ፈጥሮ መንግሥት መመስረቱ የሚታወስ ነው፡፡
በፓርቲዎቹ መካከል የተደረሰው ስምምነት ስራ ላይ እንዲውል የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላትን ይሁንታ ማግኘት አለበት፡፡ 460ሺ የሚሆኑ የፓርቲው አባላትም ድምፃቸውን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እ.አ.አ በ2013 የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ከመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ፓርቲ ጋር ጥምረት ፈጥሮ መንግሥት ለመመስረት በተደረገው ድርድር 76 በመቶ የሚሆኑት የፓርቲው አባላት ጥምረቱን ደግፈው ነበር፡፡
የአልጀዚራው ዘጋቢ ፖል ብሬናን ከበርሊን እንደዘገበው፣ ዘንድሮ ጥምር መንግሥት ለመመስረት በሚደረገው ጥረት የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ፖለቲከኞች ከፓርቲው አባላት ትልቅ ተቃውሞና ፈተና ይጠብቃቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተለይ ደግሞ ወጣት የፓርቲው አባላት የጥምረቱን ስምምነት በቀላሉ ይቀበሉታል ተብሎ እንደማይገመትና በፓርቲ አመራሮች ደረጃ የተደረሰው ስምምነት ይሁንታ ቢያገኝም ለስምምነቱ ድጋፋቸውን በሚሰጡትና ስምምነቱን በሚቃወሙት አባላት ቁጥር መካከል ሰፊ ልዩነት እንደማይኖር ይገመታል፡፡
ባለፈው መስከረም በጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ተደርጎ ውጤቱ ከታወቀ በኋላ የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ፖለቲከኞች ፓርቲያቸው ከወግ አጥባቂው የመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ፓርቲ (ክርስቲያን ዴሞክራሲያዊ ኅብረት) ጋር ጥምር መንግሥት መመስረት እንደማይፈልግ ገልፀው ነበር፡፡
የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ኃላፊዎች ሃሳባቸውን ቀይረው ከወግ አጥባቂው የመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ፓርቲ ጋር ጥምር መንግሥት ለመመስረት ፍላጎት ያሳዩትና የተስማሙት የመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ፓርቲ ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመስማማት ጥምር መንግሥት ለመመስረት ያደረገው ሙከራ አለመሳካቱን ተከትሎ ነው፡፡
ባለፈው መስከረም ወር በተደረገው ምርጫ ‹‹ኦልተርኔቲቭ ፎር ጀርመን የተባለ የፖለቲካ ፓርቲ አሁን ጥምር መንግሥት ለመመስረት ከተስማማ ከክርስቲያን ዴሞክራሲያዊ ኅብረት ፓርቲ እና ከሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ በመቀጠል ሦስተኛውን አብላጫ ድምፅ ማግኘቱ ጥምር መንግሥት ለመመስረት ለተስማሙት የፖለቲካ ፓርቲዎች ልኂቃን ራስ ምታት እንደሆነባቸው ይነገራል፡፡
ስምምነቱ በሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ይሁንታ (አብላጫ ድጋፍ) ካገኘ በቀጣዩ ወር ማርቲን ሹልዝ የፓርቲውን ሊቀ መንበርነታቸውን ለቀው የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይሆናሉ፡፡
(የመረጃው ምንጮች ፡ አልጀዚራ፣ ቢቢሲ እና ዶቼ ቬሌ ናቸው)

አንተነህ ቸሬ

 

Published in ዓለም አቀፍ

ከእናቷ እቅፍ የወጣች ጫጩት፤
የራበው ጭልፊት ቢሞጨልፋት፤
የማነው ስህተት፤ የማነው ጥፋት፤
የእናት፤ የጫጩት ወይስ የጭልፊት?
ይችን መንደርደሪያ ስንኝ የተጠቀምኩት ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታና የገባንበትን ወቅታዊ አዙሪት ፍንትው አድርጎ ያሳያል ከሚል ግለሰባዊ እሳቤ የተነሳ ነው፡፡ ጭልፊቱ ጫጩቷን ቢወስድ እርቦት ይሆናል፡፡ ጫጩቷ ደግሞ ካለማወቅ ከእናቷ ጉያ ወጥታ ይሆናል፡፡ እናቲቷም ጫጩቷ ፀሐይ እንድትሞቅ አስባ ይሆናል፡፡ ወይ ደግሞ እናቲቷ ጠላት በቅርብ አለ ወይም የለም የሚለውን እሳቤ ዘንግታ ይሆናል፡፡ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ብቻ በዚህ የሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ የሆነ ስህተት ተፈፅሟል፡፡ ጫጩቷ እስከ ወዲያኛው አሸልባለች፡፡ ጭልፊቷም ለጊዜው ጠግባለች፡፡ እናቲቷም በልጇ መሞጭለፍ ተክዛለች፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ ተዋናዮቹ በርካቶች መሆናቸውን መረዳት እንችላለን፡፡ በአገራችን ነባራዊ ሁኔታም ይህ ምስል ይታየኛል፡፡ ይሁንና እናቲቷ ለቀሩት ጫጩቶቿ ሁሌም ማሰቧ አይቀርም፡፡ ስለቀሪዎችም አብዝታ መጨነቋ ግድ ይላታል፡፡ ጭልፊቷም ብትሆን ቀን ጠብቃ አድፍጣ ሌላ ጫጩት ለቀም አድርጋ ለመውሰድ ማዘናጋቷ አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ ጥፋትም፤ ትምህርትም አለ፡፡ አገራችን እንዲህ ናት፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ስላለፈው መቆጨታችን ግድ ይለናል፡፡ ስለሚመጣውም ማሰባችን ተፈጥሯዊ ግዴታ ነው፡፡ እያዘናጉን ወደ ባሰ ችግር የሚከትቱን ነገር እንዳይኖርም መጠንቀቁ ግድ ነው፡፡
ለመሆኑ በአገራችን የተከሰቱትና በመከሰት ላይ ያሉ ችግሮች ከምን የመነጩ ይሆኑ? ለችግሩ በርካታ ተዋናዮችን መጥቀስ እንችላለን፡፡ ህዝብ፣ መንግሥት እና ተቋማት ቀዳሚውን ድርሻ ሊወስዱ ግድ ይላል፡፡ በአገሪቱ የሙስና መንሰራፋት፤ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የተዛቡ አመለካከቶች እና ፀረ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች በመንሰራፋ ታቸው አገሪቱን ችግር ውስጥ አስገብተዋታል፡፡ ለእዚህ ደግሞ በጥቂቱም ቢሆን ሁሉም አካል ድርሻ እንዳለው መመልከት ተገቢ ነው፡፡
በአገሪቱ ውስጥ በተፈጠሩ ችግሮች አመራሩ ቀዳሚውን እንደሚወስድ መንግሥት በተደጋጋሚ መግለፁ ይታወሳል፡፡ አንዳንድ አመራሮች ህዝብ የሚጠይቀውን ይከለክላሉ እንጂ ስለምን እንደሚከለክሉ እንኳ ለራሳቸውም አይገባቸውም፡፡ የተቀመጡበትን የተደላደለ ወንበር ምቾት መጠበቅ እንጂ ወንበሩ የህዝብ እንደሆነ ይዘነጋሉ፡፡ በየጊዜው ስለሚቀያይሩት ዘመናዊ መኪና እንጂ፤ በባዶ እግር ስለሚሄደው ማህበረሰብ ከቶውንም አይጨነቁም፡፡ ለዘመናት በጨለማ ውስጥ ተውጦ በኩበት ጭስ ታፍኖ ስለሚኖረው አርሶ አደር ሳይሆን፤ ለአንዲት ደቂቃ በሰፈራቸው የጠፋው መብራት ራስ ምታት ይሆንባቸዋል፡፡
ነገሩ «አልተገናኝቶም» ሆኖ፤ በየጊዜው አዳዲስ ችግሮች ሲፈጠሩ አዲስ መፍትሄ ሳይሆን ጥንት የነበረውን መፍትሄ እና አሰራር ለመተግበር ይሞከራል፡፡ ይህ ደግሞ ከትርፉ ኪሳራው እጅጉን የበዛ ከመሆኑ ባሻገር «በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ» ይሉት የአበው ብሂል ሆኖ በዚያው ይዳፈናል፡፡
ከሕዝብ ጥቅም የራሳቸውን ማስቀደምን ምርጫ የማድረግ አስተሳሰብ የያዙ አንዳንድ አመራሮች ስህተታቸውን ፍንትው አድርጎ የነገራቸውን ባለሙያ በምላሳቸው ውስጥ አስገብተው መልሰው መላልሰው ያላምጡታል፡፡ ቀን ጠብቀው በደህና ለበቅ ይለበልቡትና ናላውን ያዞሩታል፡፡ ይህ በአገራችን ለዘመናት ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ ሊላቀቀን ያልቻለ የበቀል ባህላችን ነው፡፡ በእርግጥ ችግራችንን የሚነግረን ሰው አላጣንም፡፡ መፍትሄ ማበጀት፣ አዳዲስ አስተሳሰቦችን ማራመድ እና ከነገው አስተሳሰብ ጋር የሚራመድ ትውልድ መፍጠር ተሳነን እንጂ፡፡
የተራበን ሕፃን ልጅ በአንቀልባ ተሸክመው ከጀርባ ላይ አስተኝተው አሊያም ከመሬት አውርደው በዕቃ ዕቃ ጨዋታ እያጫወቱት እሽሩሩ ማሙሽ ቢሉት ከቶውንም ረሀቡን አያስታግስለትም፡፡ ይልቁንም በርሃብ የተራቆተ እንጀቱን ማባባስ፤ ድካሙን መጨመር እንጂ፡፡ አንዳንድ አመራሮች ሰዎች የሚያምኑበትን ሃሳብ ትተው «እኔ የምለውን ብቻ ስሙ» ብለው የሙጥኝ የሚሉ በየቦታው ተበራክተዋል፡፡ ቢሆን ቢሆን ሃሳብ በሃሳብ ላይ እያፈለቁ፤ አሸናፊ ሃሳብን ማንሸራሸር በተገባ ነበር፡፡ ይህ ማለት ግን ህግ፤ ደንብ እና መርህ ተከትለው የሚሠሩ ልሂቃን የሉም ማለት አይደለም፤ በጣት የሚቆጠሩ ሆኑ እንጂ፡፡
በእርግጥ ለአገሪቱ ዜጎች መተማመኛ የሚባሉ ተቋማትም አሰራራቸው ሊፈተሽ ግድ ይላል፡፡ ባለሥልጣናት በሥልጣናቸው እንዳይባልጉ፤ በሙስና እንዳይዘፈቁ ከበላይ ሆነው እንዲከታተሏቸው የተሰየሙ አካላትና ተቋማት ከወዴት ነበሩ የሚለውንም ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡ የህዝብ እንባ እንዳይፈስስ እንባ አባሽ ተቋማት በራቸው ክፍት ነበር ወይስ ክርችም አድርገው ዘግተውታል ወይንስ ሳይዘጉትም ሳይከፍቱትም ገርበብ አድርገው ትተውታል? ብሎም መጠየቅ አንድ ጉዳይ ነው፡፡
ተቋማት የተበጀተላቸውን ገንዘብ እንዴት እና ለምን ዓላማ ተጠቅመዋል? ብሎ የሚከታተል ተቋምስ እስከምን ድረስ ጥረት አድርጓል? ፍትህ ሲዛባ ሚዛናዊ እና አስተማሪ የሆኑ ውሳኔዎች እየተሰጡ ይሆን ብሎ መጠየቅም ሀቅ የተሞላበት የመፍትሄ አንዱ ጅምር ሊሆን ይገባ ነበር፡፡ ስንቶችስ ቀልጣፋ አገልግሎት አግኝተው ስንቶችስ ድምፃቸው ተውጦ ቀርቷል? የሚለውንም መቃኘት ያስፈልጋል፡፡ ለመሆኑ አገርን ያክል የሚመራ ፓርቲ እና ድርጅትስ ስለምን እነዚህ ሥርዓት አልበኞችን እና በሥራቸው የማይተማመኑ ዳተኞችን ሊታገሳቸው ወደደ? ስንል በጥልቅ ስሜት እና ቁጭት መጠየቅ አለብን፡፡
በእርግጥ በአገራችን ለሚስተዋሉ ችግሮች የህዝቡም ድርሻ ቀላል አይደለም፡፡ ለመሆኑ ህዝቡ ሙሰኛ አመራሮችን በጉያው ተሸክሞ መቆየቱስ ስለምን ይሆን? ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ በማወቅ ወይስ ባለማወቅ? ካለማወቅ ከሆነ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ጥያቄዎች እንዴት እንደ አሸን ሊፈልቁ ቻሉ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፤ ይገባልም፡፡ በማወቅስ ከሆነ ስለምን እስካሁን ድረስ ትዕግስት አስፈለገ የሚለውን ማስተዋል ይገባል፡፡ ከዚህም ባለፈ እንደ ህዝብ ሊነሱ የሚችሉ በርካታ ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
በእኔ እምነት አሁን በአገራችን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በርካታ ችግሮች የሚስተዋሉት በአገር አቀፍ ያሉ የመንግሥት ተቋማት፤ አመራሮች እና ሲቪል ሰርቫንቱ ተገቢውን ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው ነው፡፡ የህዝብን ችግር ሊያቃልሉ የሚችሉ ተቋማት ኃላፊነታቸውን በብቃት ባለመወጣታቸው የተፈጠረ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ከሆነ ታዲያ ብዙ መሥራት ግድ ይላል ማለት ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት በአግባቡና በተጠናከረ መልኩ የማይሠሩ ከሆነ ህንፃዎችን ብቻ መደርደር አግባብ አይደለም፡፡ በመሆኑም የህዝቡን ንቃተ ህሊና ከፍ የማድረግ ሥራ ማከናወን አስፈላጊ መሆኑንም ያመላክታል፡፡
ህዝቡ ስብሰባ እንዲወጣ ብቻ ሳይሆን በስብሰባ ላይ የሚያነሳቸውን መልካም ጅምሮችን ማጠናከር ህጸፆች እንዲታረሙና የተለያዩ ሃሳቦች እንዲንሸራሸሩ ዕድል ሊኖር ይገባል፡፡ በእርግጥ በጅምር ደረጃ እነዚህ ነገሮች የሉም ማለት ባይቻልም፤ በተፈለገው ደረጃ አልዳበሩም፡፡ አንዳንድ የበላይ አመራሮች ቃሌ ሕያው ነው ብለው ራሳቸው ጀምረውት፤ ራሳቸው የሚያሳርጉበት አካሄድን መፈተሽ ሲቻል ነው መፍትሄ የሚመጣው፡፡ ይህ አይነት አካሄድ ቤት ሳይኖረው ቁልፍ እንደሚገዛ ደንበኛ ያስቆጥረዋል፡፡
ችግሮችን ከማውራትም በዘለለ ለችግሮች መንስዔ ስለሆኑት ነገሮች ቅድሚያ ማሰብ አለብን፡፡ ስንጠየቅ ብቻ ሳይሆን እንደምንጠየቅም ማወቅ አለብን፡፡ ህዝቡ አሳውቁን ብሎ ሲያፋጥጠን ብቻ ሳይሆን ማወቅ ስላለበት ቀድሞ ማሳወቅ እንደ ግዴታም፤ ባህልም መታየት አለበት፡፡ በዚህም ለችግሮች መፍትሄ ልናበጅላቸው እንችላለን፡፡
ሕዝቡም ቢሆን ችግሮችን ለዘመናት ተሸክሞ ከመኖር ይልቅ በወቅቱ ችግሮችን የሚያሳውቅበት፤ የሚታገልበትና ራሱም የመፍትሄ አካል የሚሆንበት ግልጽ አሰራር መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ የህዝብን ንቃተ ህሊና ሊያነቁ በሚችሉ ተግባራት ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሙሰኞችን የሚታገል ማህበረሰብ ማፍራት ብቻ ሳይሆን፤ ህዝብ በሚሰጠው መረጃ እና ማስረጃ ላይ በመመስረት እውነቱን እንዲያውቀው ማድረግ ይገባል፡፡ በእርግጥ ችግር ሳይኖር መፍትሄ፤ መፍትሄ ሳይኖር ችግር ያለ አይመስለኝም፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን በሚፈጠሩ ችግሮች ልክ መፍትሄ ማበጀት ይገባል፡፡ ቢሆን ቢሆን ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ቀድሞ በመገንዘብ የመፍትሄ አካል መሆን እጅጉን የተሻለ ነው፡፡ ዝናብ የሚያስገባ ቤትን ለመጠገን የግድ የክረምት ዝናብ መጥቶ ጎርፍ ማየት ተገቢ አይመስለኝም፤ ቀድሞ መጠገን እንጂ፡፡
ወደ ዋናው ነጥቤ ስመለስ ጫጩቷ ስለመወሰዷ ብቻ ሳይሆን፤ መቼ፣ ለምን፣ እንዴት፣ በማን እና የት እንደተወሰደች በሚገባ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ችግሩን ከተገነዘቡ በኋላ ደግሞ ለመፍትሄው በሰፊውና በሆደ ሰፊነት ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ስለጠፋው ብቻ መብከንከን ብቻውን መፍትሄ አይሆንም፡፡ ይልቁንም ዳግም የተባባሱ ችግሮች እንዳይከሰቱ ቀዳዳዎችን መድፈን ያስፈልጋል፡፡ ጫጩቷን ለማዳን ቢቻል ጭልፊቷን ማስወገድ የመጨረሻው አማራጭ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ባይሆን እንኳን በቅርብ ያለችውን ጫጩት እንዴት ማዳን እንደሚቻል ማሰብ ተገቢ እና አግባብም ነው፡፡ በቃ አገራችንም እንዲህ ናት፡፡ የመፍትሄው መጨረሻ ድህነትን ማጥፋት ነው፡፡ ይህ በአንድ ሌሊት እንደማይሆን ስለምናውቅ፤ ግን ደግሞ ወደ መሮጫው መም እየገባን ስለሆነ ወደለየለት ድህነትና ጉስቁልና የሚያስገባንን ሰፊ መንገድ መዝጋት ይገባናል፡፡ ችግር ሳይኖር መፍትሄ፤ መፍትሄ ሳይኖር ችግር የለምና!

እንፆኪ ዘሲያደብር 

Published in አጀንዳ

ኢትዮጵያ ለበርካታ አሥርት ዓመታት በድርቅ፣ በድህነትና በጦርነት ስትደቆስ የኖረች አገር ለመሆኗ የህዝቦቿ ጉስቁልና እና የነበራት የኋልዮሽ ጉዞ መገለጫዋ ናቸው፡፡ በተለይም ለበርካታ ዓመታት የዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ያስከተለው ውድመት ከሰው ሕይወት በተጨማሪ ለአገር ግንባታ ይውል የነበረ አንጡራ ሀብቷን በማባከን ሕዝቡን ለድህነት ዳርጓል፡፡
ለነፃነትና ለዴሞክራሲ ሲባል በተካሄደው እልህ አስጨራሽ ትግል በተገኘው ድል የሰላም መስፈን፣ የዴሞክራሲ ጭላንጭልና የልማት ጅማሬ ተፈጥሮ ከነበረችበት ችግር ወደ ዕድገትና የተሻለ ደረጃ እየተሸጋገረች ነው፡፡
አገሪቱ እስካሁን ላስመዘገበችው ዘርፈ ብዙ ፍሬያማ ውጤቶች የምትከተለው የፌዴራል ሥርዓት መሠረት መሆኑም በተጨባጭ ተረጋግጧል፡፡ የነበሩት ችግሮች መፈታት የቻሉትም በፌዴራል ሥርዓቱ ነው። አንዳንዶች ለራሳቸው የፖለቲካ ጥቅም ሲሉ የፌዴራል ሥርዓቱን በመኮነን ነባራዊውን ሃቅ ሸፍነው ድሮም የነበሩ ትናንሽ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን የፌዴራል ሥርዓቱ ችግር አድርገው ቢያቀርቡም ሥርዓቱ ችግርን የሚያስወግድ እንጂ መንስዔ እንደማይሆን ልቦናቸው ያውቀዋል።
እንደ እውነቱ ከሆነ የፌዴራል ሥርዓቱ ካስገኛቸው በርካታ ጥቅሞች ይልቅ በየመንደሩ የሚነሱ የግጦሽ መሬትና የአካባቢያዊ የወሰን ግጭቶችን በማነፍነፍ የሥርዓቱ ውጤት አድርገው በማቅረብ ኢምንት ችግሮችን ለፖለቲካ መቀስቀሻ አጀንዳቸው ሲያውሉት ይስተዋላል።
ኢትዮጵያ የብዙ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ እንዲሁም ኃይማኖቶች ተቻችለውና ተፋቅረው የሚኖሩባት አገር መሆኗ የሚያስቀናቸው፣ ሰላም ሰፍኖባት በልማት ጎዳና ላይ መገኘቷ የሚያበሳጫቸው፣ ሥልጣንን ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ ለራሳቸው በማድረግ የግል ኑሮአቸውን ለማደላደል በግልፅ በሌሎች መስዋዕትነት ለማግኘት ያደፈጡና ያልተሳካላቸው መሰሪዎች ሕዝብን ከመንግሥት ለማጋጨት የማይፈነቅሉት ድንጋይ፤ የማይወጡት ተራራ የለም፡፡ ሆኖም ሃሳባቸው አልተሳካም።
በርግጥ አንድን አገር የሚመራ መንግሥት ልዩ ልዩና በርካታ አስተሳሰብ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን እያስተዳደረ ሁሉም ክንዋኔዎቹ አልጋ በአልጋ ይሆናሉ ብሎ ማሰብ በራሱ የዋህነትም፤ አለማወቅም ስለሚሆን ረጋ ብሎ በማሰብ አስተዋይ መሆንን ይፈልጋል፡፡
አገርን ማስተዳደር አርቆ አሳቢነትን፣ ሆደ ሰፊነትን እንዲሁም ቆራጥነትን የሚጠይቅ ቢሆንም ይህ ሁሉ ሊሟላና የተስተካከለ አመራር ሊኖር የሚችለው በኃላፊነትና በየደረጃው የተቀመጡ ሁሉ ኃላፊነታቸውን አውቀው አገልግሎታቸውን ለሚጠብቁ ወገኖቻቸው የላቀ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ አገሮች የሚከሰቱት ግጭቶች እልባት እንዲያገኙ መፍትሄ በማፈላለግና ሰላም አስከባሪ ኃይል በመላክና ሰላምን በማስፈን፣ ሽብርተኝነትን በመዋጋት፤ በአካባቢ ጥበቃ፣ በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፣ በታላላቅ ጉባዔዎች መወከል፣ ታላላቅ ጉባዔዎችን ለማስተናገድ መመረጥ መቻሏና በብቃት ኃላፊነቷን መወጣቷ አድናቆትን አስገኝቶላታል። እነዚህ ታላላቅና ድንቅ ሥራዎች ሊከናወኑ የቻሉት ባለው ሰላም በመጠቀም በመሆኑ ለሰላም መቆም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ ወቅቶች በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት የሰላም እጦት መከሰቱ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ቅሬታ ያላቸው ዜጎች ያነሱት ጥያቄ ተገቢነትን ለመመርመር፣ መፍትሄ ለመስጠትና የወደፊቱን አቅጣጫ ለመቀየስ አገሪቱን የሚያስተዳደረው ፓርቲ ኢህአዴግ ረዘም ላሉ ቀናቶች ጥብቅ ውይይት አካሂዶ የራሱን ጉድለት በመለየት፣ የሚታረመውን ለማረም፣ የማይበጁ ተግባራትን ለማስወገድ፣ በቀጣይ ለሕዝብና ለአገር ዕድገት የሚበጅ ተግባር ለማከናወን አዲስ አቅጣጫ እንደቀየሰና በቁርጠኝነት መነሳቱን አመላክቷል፡ ይህ ይበል የሚያሰኝ በመሆኑ በሁሉም በመንግሥት የሥራ ኃላፊነት የተቀመጡ ሁሉ ለውጤታማነቱ ያላሰለሰ ድጋፋቸውን ሊሰጡት ይገባል፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።