Items filtered by date: Thursday, 01 March 2018

በወርሃ የካቲት መጀመሪያ በሩዋንዳ ኪጋሊ በተሰናዳው የዘንድሮው 16ኛው የአፍሪካ ብስክሌት ቻምፒዮና ኢትዮጵያ በ13 ሜዳሊያዎች ሁለተኛ ደረጃ አግኝታ ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡ በውድድሩ ተሳትፋ በአዋቂዎች የብስክሌት ግልቢያ ለአገሯ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘችው ሰላም አመሃ፤ አጠቃላይ ውጤቱ ያለፌዴሬሽን በቂ ድጋፍ የተገኘ በመሆኑ በጣም ደስተኛ መሆኗን ትገልጻለች፡፡ ወደ ብስክሌት ስፖርት ከገባች ሦስት ዓመት ያልሞላት ሰላም፤ ከዚያ በፊት በእግር ኳስ ስፖርት ስትሳተፍ ቆይታለች፡፡
‹‹ብስክሌት ስፖርት በክለቦች ጥሩ እንቅስቃሴ ቢኖረውም በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ብዙ ይቀረዋል›› የምትለው ሰላም፤ ብስክሌት ከሌሎች ስፖርቶች አንፃር የሚሰጠው ትኩረት በጣም አነስተኛ ነው፡፡ እንደእርሷ ሃሳብ፤ ተወዳዳሪዎች ከአህጉራዊ ውድድሩ በፊት በቂ ዝግጅት አላደረጉም፡፡ ለዚህ ምክንያት የምትለው ደግሞ ተወዳዳሪዎች አብረው በአንድ ካምፕ ተሰባስበው ልምምድ አለመስራታቸው ነው፡፡ በግብዓት በኩልም ከትጥቅ ጀምሮ እስከ ብስክሌት ድረስ በቂ ድጋፍ አይደረግም፡፡ የሌሎች አገሮች ተሞክሮ ግን ከኢትዮጵያ ብዙ የተራራቀ መሆኑንም ከውድድሩ ቆይታዋ ታዝባለች፡፡
ኢትዮጵያ ለብስክሌት ስፖርት እንግዳ አይደለችም፡፡ እ.አ.አ በ1956 ሜልቦርን ኦሎምፒክ በዝነኛው ብስክሌተኛ ገረመው ደምቦባ ተሳትፋለች፡፡ በመካከል የነበሩ የኦሎምፒክ ውድድሮችን በዘርፉ ከታዛቢነት ያልዘለለ ተሳትፎ ያልነበራት ኢትዮጵያ ዳግም የኦሎምፒክ ውክልናዋን በብስክሌት ያረጋገጠችው እ.አ.አ በ1972 የሙኒክ ኦሎምፒክ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በዚህ ውድድርም የስፖርተኞች ቁጥር ወደ አምስት አድጎ ነበር፡፡ ከሙኒኩ መድረክ በኋላ ኢትዮጵያ በብስክሌት ውድድር ኦሎምፒክ ላይ ለመሳተፍ 44 ዓመት መጠበቅ ግድ ብሏታል፡፡
በኪጋሊ የተካሄደውን የአፍሪካ ሻምፒዮን የኢትዮጵያ የሴት ብስክሌት ቡድን የመሩት አሰልጣኝ ተከስተ ጥላሁን፤ እንደ አገር ስፖርቱ ካለው ረጅም ታሪክ አንፃር የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ እንደ እርሳቸው ሃሳብ፤ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ካለበት የበጀት ውስንነትና ከሌሎች አገሮች የተሻለ ዝግጅት አድርጎ ወደ ውድድሩ ከመግባት አንፃር ኢትዮጵያ በኪጋሊ ያስመዘገበችው ውጤት ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይም በዋናነት አህጉራዊ ውድድሮች በመደገፍ በኩል የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ኃላፊነት ቢሆንም በትኩረት ማነስ ምክንያት ለውጡም አዝጋሚ ሆኗል፡፡
‹‹በስፖርቱ ላይ በዋናነት የቁሳቁስ እጥረት አለ›› የሚሉት አሰልጣኝ ተከስተ፤ ለአንድ ስፖርተኛ ሁለት ብስክሌት ከማስፈለጉ ባሻገር የአንዱ ዋጋም ቢሆን ውድ በመሆኑ ለስፖርተኞች አስቸጋሪ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ በዚህም ምክንያት በአፍሪካ ደረጃ 15 የሚሆኑ ውድድሮች ቢኖሩም ኢትዮጵያ የምትሳተ ፈው በሁለቱ ብቻ ነው፡፡ እነሱም የጋቦን እና የሩዋንዳ ናቸው፡፡ ይሄ ደግሞ በቀጥታ ከስፖንሰር ሺፕና ከተለያዩ ድጋፎች እጥረት ጋር ይገናኛል፡፡
ባለፈው የኪጋሊ ውድድር ከኢትዮጵያ በሰባት ሜዳሊያዎች በመብለጥ አንደኛ ሆና ያጠናቀቀችው ኤርትራ ነበረች፡፡ በውድድሩ ሃያ ሜዳሊያዎችን አግኝታለች፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ምን ይሆን? ለሚለው ጥያቄ ‹‹ኤርትራውያን ውድድሩን በበላይነት ካጠና ቀቁ በኋላ ወደ አገራቸው ሲመለሱ አቀባበል ያደረጉ ላቸው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ናቸው›› የሚሉት አሰል ጣኝ ተከስተ፤ ይሄ ለስፖርቱ የሰጡት ትኩረት ከፍተኛ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ የትኩረቱ ማነስም የብስክ ሌት ስፖርተኞችን ተስፋ የሚያስቆርጥ ይሆናል፡፡
በመሆኑም ይላሉ፤ ከአደረጃጀት ጀምሮ ስፖርቱ ላይ ማሻሻያዎችን በማድረግ የውድድር ሂደቶችም ብሔራዊ ቡድኑን ሊያጠናክር በሚችል መልኩ ሊቀረፅ ይገባል፡፡ ያለፈውም የሩዋንዳ ውድድር የክለቦች ድጋፍ ባይኖር እንኳንስ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ይቅርና ተሳታፊ ለመሆን በራሱ ፈታኝ ይሆን ነበር፡፡ በመሆኑም ልክ ክለቦችን እንደሚደግፉ ተቋማት ሁሉ መንግሥትም ለስፖርቱ የሚያደርገው ድጋፍ ማደግ አለበት፡፡
ብስክሌት ስፖርት ሲነሳ እንደ ክልል ከውጤት ጋር ቀድሞ የሚነሳው ትግራይ ክልል ነው፡፡ በመቀጠል በአማራ ክልል የተሻለ ትኩረትና እንቅስ ቃሴ መኖሩን ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ በትግራይ ክልል ስፖርቱን ከሚደግፉ ተቋማት መካከል ደግሞ መስፍን ኢንዱስትሪያል ይጠቀሳል፡፡ በሩዋንዳው መድረክም ተወዳዳሪዎችን ከላኩ ክለቦች መካከል አንዱ ነው፡፡ ድርጅቱ በክልሉ ልክ እንደ ወንዶች ሁሉ የሴት ብስክሌት ተወዳዳሪዎች ቁጥር እንዲጨምር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ይገልጻል፡፡
የመስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ኪዳነማርያም አትክልት፤ ስፖርተኞቹ ከደመወዝ ጀምሮ ኢንሹራንስና የትምህርት ወጪ እንዲሁም ሌሎች ግብዓቶችን ከማሟላት ባሻገር አሰልጣኞችና የህክምና ባለሙያዎችን ቀጥሮ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ላይ ውድድሮች ሲዘጋጁም ሆነ ለተጨማሪ ስልጠናዎች ወጪያቸውን በመሸፈን ተሳታፊዎችን የሚልኩ ሲሆን፤ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አቅሙን አዳብሮ ወጪ መሸፈን እስከሚችል ድረስ ድጋፉ ይቀጥላል ባይ ናቸው፡፡
ለስፖርቱ ከሚደረገው ድጋፍ አንፃር አሁን የተገኘው ውጤት ትልቅ ነው የሚሉት አቶ ኪዳነማ ርያም፤ ነገር ግን በቀጣይ አገር አቀፉ ፌዴሬሽን አቅሙን ከማጠናከር በተጓዳኝ ክልሎችም ለስፖርቱ የሚሰጡት ትኩረት ካላደገ የተጀመረውን ማስቀጠል ይከብዳል፡፡ በመሆኑም ስፖርቱ ላይ በድጋፍ የመሳተፍ ፍላጎት ያላቸውን ድርጅቶች መጋበዝ እንዲሁም ግብዓቶችን ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ ያኔ አሁን የተጀመረው አበረታች ተስፋ ጎልብቶ ማየት ይቻላል፡፡
የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ወርቁ ገዳ፤ እንደ አገር ስፖርቱ አሁንም የሚሰጠው ትኩረት ብዙ ቢቀረውም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአህጉር የተሻለ ውጤት ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ እየተሰራ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በዚህም አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸ ውን በመጥቀስ፡፡ ተወዳዳሪዎች የተሻሉ ስልጠናዎችን በባህር ማዶ አገሮች እንዲያገኙ ከማድረግ ጎን ለጎን በአገር ውስጥ እንደ ‹‹ቱር መለስ›› ያሉ ውድድሮች በማዘጋጀት ስፖርቱ ይበልጥ ትኩረት እንዲያገኝ ተደርጓል ይላሉ፡፡
በተጫዋቾችና በአሰልጣኞች በኩል ‹‹የግብዓት ችግር አለ›› በሚል ለሚነሳው ጥያቄ፤ የፌዴሬሽኑ ዋና ተልዕኮ ክልል ፌዴሬሽኖችን መደገፍ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ስፖርቱ እንዲስፋፋ መስራትና ዕድሎችን ማመቻቸት እንጂ ግብዓት ማሟላት አይደለም የሚል ምላሽ አላቸው፡፡ ለዚህም ክለቦች የራሳቸውን ከማሟላት ባሻገር የክልል ፌዴሬሽኖች ሚና ቢጎላም ከግብዓት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ግን ችግር መኖሩን ያምናሉ፡፡ ለውድድር የሚሆኑ ዘመናዊ ብስክሌቶችና ተያያዥ ትጥቆች በአገር ውስጥ ስለማይቀርቡ ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን የተለያዩ ትጥቅ አቅራቢዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ጥረት ተጀምሯል፡፡
የአገር ውስጥ ውድድር የተሻለ ለማድረግም በአገሪቱ የተለያዩ ክለቦች የሚሳተፉበት ውድድር ለማዘጋጀት ታቅዷል፡፡ ማበረታቻን በተመለከተ ለሚነሳው የስፖርተኞች ቅሬታ ግን ‹‹እርሱ የእኛም ጥያቄ ነው›› የሚሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ አምናም ቃል ተገብቶ ማበረታቻ ያልተደረገ ሲሆን ዘንድሮ እንዳይደገም ግን ከወዲሁ ጥረት ተጀምሯል፡፡ በቀጣዩ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የሚዘጋጀውን ውድድር በተመለከተ ‹‹ዕድሉ በእጃችን የገባ ነው›› ያሉት አቶ ወርቁ፤ ኢትዮጵያ ማዘጋጀቷ በብዙ ዘርፎች ከመሳተፏ ባሻገር ከሁለት ዓመት በኋላ ለሚደረገው ኦሎምፒክም ብቁ ስፖርተኞችን ለመምረጥ ያስችላል፡፡

ብሩክ በርሄ

Published in ስፖርት

የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ከዛሬ ጀምሮ እስከ ፊታችን እሁድ ድረስ ለአሥራ ሰባተኛ ጊዜ በእንግሊዝ በርሚንግሃም ከተማ ይካሄዳል። ኢትዮጵያም በአምስት የውድድር ዓይነቶች በሁለቱም ፆታ ተሳታፊ ለመሆን ልዑካን ቡድኗን ባለፈው ሰኞ ከሌሊቱ አምስት ሰዓት ላይ ወደ ሥፍራው ልካለች። ውድድሩ ዛሬ ሲጀመር ከረፋዱ 5ሰዓት ከ15 ላይ በሚካሄደው የሴቶች የሦስት ሺ ሜትር ፍፃሜ ውድድርም የመጀመሪያው የወርቅ ሜዳሊያ ይመዘገባል ተብሎ ይጠበቃል። 

በዚህ ውድድር በቻምፒዮናው ሦስት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ከዚህ ቀደም መሰብሰብ የቻለችው አትሌት ገንዘቤ ዲባባ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ የማስመዝገብ ሰፊ ዕድል እንደሚኖራት ተገምቷል። ከሦስት ሳምንታት በፊት በስፔን ሳባዴል በርቀቱ 8፡31፡23 የሆነ የዓመቱ ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ የቻለችው ገንዘቤ በቤት ውስጥ ውድድሮች ካስመዘገበቻቸው በርካታ ክብረወሰኖችና ድሎች አኳያ ያላት ሰፊ ልምድ ሲደመር በውድድሩ የወርቅ ሜዳሊያ ግምቱ ወደ እሷ ቢያዘነብል አይገርምም።
ገንዘቤ ምንም እንኳን ባለፈው ዓመት በለንደን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ከጉዳት ጋር በተያያዘ ያልተጠበቀ አስከፊ ውጤት ቢገጥማትም ዘንድሮ በፍጥነት አገግማ በዓለም የቤት ውስጥ የዙር ውድድሮች አስደናቂ ብቃት ማሳየቷ ይታወቃል። ይህም በለንደኑ ቻምፒዮና ያመለጣትን ድል አስመዝግባ ቅር የተሰኙ አድናቂዎቿን እንድትክስ ዕድል ፈጥሮላታል። ገንዘቤ ባለፈው ወር በቤት ውስጥ ውድድሮች በቀናት ልዩነት በአንድ ሺ አምስት መቶና በሦስት ሺ ሜትሮች ፈጣን ሰዓቶችን በማስመዝገብ ተፎካካሪዎቿ ላይ ፍፁም የበላይነት ወስዳ ያሸነፈችበት መንገድ በዛሬው ውድድር በርካቶች እርግጠኛ ሆነው የወርቅ ሜዳሊያውን እንዲያጠልቁላት አስገድዷቸዋል። የሦስት ሺ ሜትር የቤት ውስጥ የዓለም ክብረወሰን 8፡16፡16 በሆነ ሰዓት ከአራት ዓመት በፊት ስዊድን ስቶክሆልም ላይ ማስመዝገብ የቻለችው ገንዘቤ በዛሬው የዓለም ቻምፒዮና ፉክክሯ ምናልባትም ከሌሎች አትሌቶች ጋር ሳይሆን ከራሷ ክብረወሰን ጋር ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ተገምቷል። በዚህ ርቀት ከገንዘቤ ጎን ለጎን ወጣቷ አትሌት ፋንቱ ወርቁ ኢትዮጵያን ወክላ የምትሰለፍ ሲሆን ሜዳሊያ ውስጥ ይገባሉ ተብለው ከሚጠበቁ አትሌቶችም አንዷ ነች።
ገንዘቤ ዛሬ የወርቅ ሜዳሊያውን ካሳካች በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ታሪካዊ ከሆኑ ቁንጮ አትሌቶች ተርታ የሚያሰልፋትን ታሪክ በወርቅ ቀለም የምትጽፍ ይሆናል። በዚህ ቻምፒዮና ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ ከወንድ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚስተካከለው የለም። በሴቶች ደግሞ መሰረት ደፋር አራት የወርቅ፤ ሁለት የብርና አንድ የነሐስ ሜዳሊያ በማጥለቅ ከየትኛውም ኢትዮጵያዊ አትሌት በላይ ትልቅ ታሪክ አላት። ገንዘቤ ዛሬ ድል ከቀናት በወርቅ ሜዳሊያ ደረጃ ከነዚህ ታላላቅ አትሌቶች ተርታ የሚያሰልፋትን ታሪክ ታኖራለች። ገንዘቤ የፊታችን ቅዳሜ 5ሰዓት 39 በሚካሄደው አንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ውድድር ተሳታፊ እንደመሆኗ በውድድሩ ማሸነፍ ከቻለች በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ታሪክ ከየትኛውም ኢትዮጵያዊ አትሌት በላይ የምትሆንበትን ስኬት የምታስመዘግብ ይሆናል።
የታላላቅ እህቶቿን ወርቃማ ኦሊምፒያኖች እጅጋየሁና ጥሩነሽ ዲባባ ፈለግ ተከትላ በመካከለኛ ርቀት የስኬት ማማ ላይ የደረሰችው ገንዘቤ ዲባባ እ.ኤ.አ 2012 ቱርክ ኢስታንቡል ላይ በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር 4፡05፡78 በሆነ ሰዓት የመጀመሪያ የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቋ ይታወሳል። ከዚያም በኋላ 2014 ፖላንድ ሶፖት ላይ በሦስት ሺ ሜትር 8፡55፡54 ሰዓት ሁለተኛ የወርቅ ሜዳሊያዋን ማጥለቅ ችላለች። ባለፈው የ2016 ፖርትላንድ ዩጂን ቻምፒዮናም በሦስት ሺ ሜትር 8፡47፡43 ሰዓት ሦስተኛ የወርቅ ሜዳሊያዋን ከቻምፒዮናው አግኝታለች።
በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ሞዛምቢካ ዊቷ የስምንት መቶ ሜትር አትሌት ማሪያ ሞቶላ እ.ኤ.አ ከ1993 እስከ 2008 ሰባት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ቀዳሚ ስትሆን፤ ሩሲያዊቷ የአራት መቶ ሜትርና አራት በአራት መቶ ሜትር ዱላ ቅብብል ከ1999 እስክ 2008 የነገሰችው ናታልያ ናዛሮቫ ተመሳሳይ ታሪክ ትጋራለች። ከ1993 እስከ 2001 በርዝመት ዝላይ ስኬት ላይ የነበረው ኩባዊው ኢቫን ፔድሮሶ በአምስት ተከታታይ ቻምፒዮናዎች ወርቅ በማጥለቅ ይታወቃል። ቡልጋሪያዊቷ ከፍታ ዘላይ ስቲፍካ ኮስታዲኖቫ አምስት የወርቅ ሜዳሊያዎች ያጠለቀች ሌላኛዋ አትሌት ናት። እውቁ የሶቬት ህብረት ከዚያም የዩክሬን ምርኩዝ ዘላይ ሰርጌ ቡቡካ፤ ኩባዊው ከፍታ ዘላይ ጃቪየር ሶቶማዮር አራት ወርቅና አንድ ነሐስ በማጥለቅ፤ ስዊድናዊው ከፍታ ዘላይ ስቲፋን ሆልም አራት የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ ከኃይሌና መሰረት ጋር ተመሳሳይ ታሪክ ይጋራሉ።
ቻምፒዮናው በመጪዎቹ ሦስት ቀናት ሲቀጥል እሁድ ንጋት 12ሰዓት ከ35 ላይ የሚካሄደው የወንዶች ሦስት ሺ ሜትር ፍፃሜ ውድድርም ከወዲሁ የስፖርት ቤተሰቦች በጉጉት ይጠብቁታል። ይህ ውድድር አስደናቂ አቋም ላይ በሚገኙትና በጠንካሮቹ ሦስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል የሚካሄድ ሲሆን ሦስቱም ሜዳሊያ ከነዚህ አትሌቶች እንደማይወጣ ይጠበቃል። የዓለም የቤት ውስጥ የዙር ውድደሮች ከወር በፊት ጀርመን ካርልሹር ላይ ሲጀመር በአስደናቂ ፉክክር ተከታትለው የገቡት ሐጎስ ገብረህይወትና ዮሚፍ ቀጄልቻ የወርቅ ሜዳሊያውን ለማጥለቅ ግምት ያገኙ አትሌቶች ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአምስት ሺ ሜትር ጀምሮ እስከ መካከለኛ ርቀቶች እጅግ ድንቅ አቋም እያሳየ የሚገኘው ወጣት አትሌት ሰለሞን ባረጋም እነዚህን አትሌቶች በእጅጉ እንደሚፈትን እያሳየ የመጣው ጠንካራ አቋም ምስክር ነው። ዮሚፍ ቀጄልቻ በርቀቱ ያለፈው ዓመት ቻምፒዮና ቢሆንም ዳግም ድሉን ለማጣጣም በአገሩ ልጆች ከባድ ፈተና እንደሚገጥመው ይጠበቃል። እነዚህ ሦስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አርባ ሺ፤ ሃያ ሺና አስር ሺ ዶላር ከውድድሩ ለማግኘት የሚያዳግታቸው የሌላ አገር አትሌት አይኖርም። ትልቁን ሽልማት ለማግኘት የሚያደርጉት ፉክክር ግን የዓለምን ክብረወሰን የሚያሻሽል ከሆነ ለአሸናፊው አትሌት ተጨማሪ ሃምሳ ሺ ዶላር ጉርሻ ሊያስገኝለት ይችላል።

ቦጋለ አበበ

 

Published in ስፖርት

ደቡብ እስያዊቷ አገር ሥሟ በመገናኛ ብዙኃን ተደጋግሞ ቢነሳ ማጠንጠኛው ግጭት አልያም ሽብር ሊሆን ይችላል፡፡ የአካባቢው ነባር ፖለቲካዊ ቀውስ ለሰላሟ እጦት መነሻ ቢሆንም፤ በውስጧ በርካታ ቀልብ ገዢ እውነት መኖሩ ይነገራል፡፡ በሕዝቦቿ ብዛት በዓለም አምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ፓኪስታን የተለያዩ ቋንቋዎች ይነገሩባታል፡፡ ይሁንና ሁርዱ እና እንግሊዝኛ የሥራ ቋንቋዎቿ ናቸው፡፡
ሰሞኑን ከአገሪቱ የተሰማው ወሬ ደግሞ በዓለም ሦስት ተናጋሪዎች ብቻ የቀሩትን ቋንቋ ያስተዋወቀ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ቋንቋው ባዴሺ ይሰኛል፡፡ በፓኪስታን ሰሜናዊ ግዛት በበረዶ በተከበበ ተራራ አካባቢ በሚገኘው ቢሺግራም ሸለቆ የሚኖሩት ሦስት አዛውንቶች «እኛ የሞትን ዕለት ቋንቋችን ይሞታል» ሲሉ ለቢቢሲው ዘጋቢ ዛፋር ስዬድ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ «በዓለም ሦስት ተናጋሪዎች ከቀሩት ቋንቋ ጥቂት ቃላትን መማር ትሻላችሁን?» ሲል የጠየቀው ዘጋቢው፤ የቋንቋው ህልውና አደጋ ላይ መውደቁን ከአዛውንቶች ስጋት ተገንዝቧል፡፡
ከተናጋሪዎቹ መካከል አንዱ የሆኑት ራሂም ጉል በዚህች ዓለም የቆዩበትን ጊዜ በቅጡ አይለዩም፡፡ ዘጋቢው ግን ዕድሜያቸው ከሰባ ዓመት መሻገሩን ይገምታል፡፡ አዛውንቱ ጉል፤ ቁጭት ባዘለ ድምፃቸው «ከአንድ ትውልድ በፊት የባዴሺ ቋንቋ በመንደሩ በስፋት ይነገር ነበር» ይላሉ፡፡ የቁጭታቸው ምንጭ ሁለት ነው፡፡ አንደኛው የቁጭት ምንጭ ቋንቋቸው የተደቀነበት የመጥፋት አደጋ ነው፡፡
አዛውንቱ እንደሚሉት፤ በጋብቻ ሊተሳሰሩ ከሌላ መንደር ወደአካባቢቸው የሚያመጧቸው ሴቶች በአብዛኛው ቶርዋሊ የተሰኘ ቋንቋ ተናጋሪ ናቸው፡፡ ታዲያ ከእነዚሁ ሴቶች የሚያፈሯቸው ልጆች አፋቸውን የሚፈቱት በባዴሺ ሳይሆን እናቶቻቸው በሚናገሩት በቶርዋሊ ቋንቋ ነው፡፡ ቶርዋሊ በአካባቢው ብዙ ተጠቃሚ ያለው ቋንቋ ነው፡፡ ይሄን ተከትሎ ቋንቋቸው (ባዴሺ) ወራሽ ማግኘት አለመቻሉ የአዛውንቶቹ ቁጭት ሁለተኛው ምክንያት ይሆናል፡፡
«ልጆቻችን የእናቶቻቸውን ቋንቋ ከእናቶቻቸው ጋር ያወራሉ፤ እኛ ታዲያ የገዛ ቋንቋችንን ከማን ጋር እናውራበት?» ሲሉ የሚብሰከሰኩት ራሂም ጉል፤ አምስት ልጆች ቢኖሯቸውም አምስቱም ልጆች የሚናገሩት የእናታቸውን ቋንቋ ነው፡፡ በተጨማሪም አዛውንቶቹ እንደ ዕድሜያቸው ሁሉ ከቋንቋቸው የተወሰኑ ቃላትን መዘንጋት መጀመራቸው ቋንቋው ለመጥፋት የጀመረውን ፈጣን ጉዞ የሚያቀላጥፍ ምክንያት ሆኗል፡፡
«እናቴ የቶርዋሊ ቋንቋ ተናጋሪ ናት፤ ቤት ውስጥ ማንም የባዴሺ ቋንቋ የሚያወራ የለም፤ ቋንቋውን ከልጅነቴ ጀምሮ ይዤ ለማደግ ዕድል አልነበረኝም፤ በመሆኑም ጥቂት ቃላትን ባውቅም ግን መግባባት አልችልም» ይላል የአንደኛው አዛውንት የበኩር ልጅ፡፡ የ32 ዓመቱ ነዋሪ «ቋንቋው ከአባቴ ጋር አብሮ የሚያልፍ በመሆኑ በጣም እፀፀታለሁ» ሲልም ሃሳቡን ያጠናክራል፡፡
በአካባቢው ምንም ዓይነት የሥራ ዕድል አለመኖሩ በኅብረተሰቡ መካከል ሊዳብር የሚገባውን የቋንቋ መስተጋብር አዳክሞታል፡፡ ይሄም አዛውንቶቹ ብቻ ለሚናገሩት ቋንቋ መዳከም ጉልህ ምክንያት አድርገው ይወስዱታል፡፡ አዛውንቶቹ ይሄን ቢሉም፤ በአገሪቱ እየጠፉ በሚገኙ ቋንቋዎች ላይ ጥናት በሚያካሂድ አንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት የቋንቋ ባለሙያ ሆኖ የሚሰራው ሳጋር ዛማን፤ ምክንያቱ ሌላ መሆኑን ነው የሚናገረው፡፡
ይሄንኑ ጉዳይ ሊመረምር ሦስት ጊዜ ወደ አካባቢው የተጓዘው ሳጋር፤ ቋንቋውን ለመጠቀም ምንም ዓይነት ፍላጎት አለመኖሩን ተገንዝቧል፡፡ ይሄም ብዙ ተናጋሪ ያለው ቋንቋ ተናጋሪዎች በባዴሺ ቋንቋ ላይ የሚፈጥሩት ማግለል መኖሩን እንዲታዘብ አድርጎታል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቃላትን መሰብሰቡን የሚናገረው የቋንቋ ባለሙያ፤ ከዚህ በመነሳትም ባዴሺ ከኢንዶ አርያን ንዑስ የቋንቋ ቤተሰብ እንደሚመደብ አረጋግጧል፡፡ «ቋንቋውን ለመታደግም በጣም ረፍዷል» ብሏል፡፡
በመዘግየቱም ምክንያት ሦስቱ የቢሺ ግራም ሸለቆ አዛውንቶች የዚህችን ዓለም ኮንትራት አጠናቀው ምድርን ሲሰናበቱ ባዴሺም መሰናበቱ የግድ ይሆናል፡፡ ያኔ ቤተሰቦቻቸው ወይም የአካባቢው ነዋሪዎች ፍራሽ የሚዘረጉት ለአንድ ሰው ሞት ኀዘን ለመቀመጥ ብቻ ሳይሆን፤ ባዴሽንም ለመሰናበት ይሆናል፡፡

ብሩክ በርሄ

Published in መዝናኛ
Thursday, 01 March 2018 18:19

የአድዋ አደራ

የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን በአድዋ ታሪክ ሲዘክረው የሚኖር ገድለ የፈጸሙበት ዕለት ነው፡፡ በዕለተ ሰንበት የተፈጸመው ጀግንነት የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን «የጥቁር ሕዝቦች ድል» እስከመባል ደርሷል፡፡ በአምባላጌ፣ መቐለና አድዋ በተደረጉ ሦስት ጦርነቶች የኢትዮጵያ ጀግኖች ወራሪውን የኢጣሊያ ጦር አሸንፈዋል፡፡ ድሉ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት፣ የአገር ፍቅርና፣ የአንድነት ተምሳሌት ሆኖ ዛሬም ይዘከራል፡፡
የጥቁር ሕዝቦች ኩራት የሆነው የአድዋ ድል ብሔራዊ በዓል ሆኖ መከበር የጀመረው ጦርነት ከተካሄደ ከሰባት ዓመታት በኋላ ሲሆን ነገ የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም 122 ዓመት ያስቆጥራል፡፡ ኢትዮጵያ በቅኝ ያልተገዛች ብቸኛ አፍሪካዊት አገር እየተባለች ከላይቤሪያም በላይ በዓለም የታሪክ መድረክ ስሟ የሚነሳው አያቶች በከፈሉት የደም ዋጋ ነውና የአሁኑ ትውልድ ወጣት አድዋን እንዴት ይረዳዋል? ከአድዋስ የተሰጠው አደራ ምንድን ነው? በማለት ወጣቶችንና የታሪክ ምሁር አነጋግረናል፡፡
ወጣት ኤርሚያስ ተረፈ ይባላል፡፡ ጀግኖች አባቶችና እናቶች ከውጭ የመጣውን ወራሪ መመከት የቻሉት ፆታና ዕድሜ ሳይበግራቸው ሁሉም በአንድ ድምፅና ልብ በመዝመታቸው መሆኑን ያወሳል፡፡ «በአድዋ ጦርነት ጨርቄን ማቄን ሳይል የዘመተው ትውልድ ወራሪን ለማባረር ነበር አሁን ደግሞ ለሁሉም ጉዳዮቻችን ውስጥ አድዋን በህብረትና በአንድነት ልናሳየው ይገባል » ይላል፡፡ እንደ አገር የማይጠቅሙንን ፅንፍ በመተው በአንድነት ማሰብ ጠቀሚ እንደሆነም ይመክራል፡፡ በአድዋ ድል በአባቶች መስዋዕትነት የመጣውን አንድነት ይህ ትውልድም እንዲቀጥል ማድረግ እንደሚገባ በማመ ልከት፡፡
ወጣት ኤርሚያስ እንደሚናገረው፤ ወጣቱ አድዋን ማወቅ ያለበት ያህል እንዲያውቅ አልተደረገም፡፡ በተለይም አባቶች በአድዋ ላይ የተቀዳጁት ድል ታላቁን ቦታ ቢይዝም፣ ቀደም ብለውና ከዚያም በኋላ የነበሩ አባቶች ኢትዮጵያን ከአደጋ ሲጠብቁ ራሳቸውን መስዋት ማድረጋቸውን በተደጋጋሚ ለወጣቱ እየተነገረም አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ሌሎች በዓላት የሚተዋወቁትን ያህል አድዋ ለወጣቱ ኩራት እንዲሆን ተደርጎ አልተሰራም፡፡
የቀደመውና የመጣበትን ታሪክ ሳያውቅ የወደፊቱን የሚያይ ትውልድ መፍጠር አደጋች እንደሆነ የሚናገረው ወጣቱ፤ በተለይም አድዋ ስኬት ከጦርነት ጀብዱነት ባለፈ በማያስችሉ ሁኔታዎች ውስጥ በፅናት ማለፍ እንደሚቻል ማሳያ በመሆኑ ስለ አድዋ በተለያየ መልኩ በማስተዋወቅ ትኩረት መስጠት ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ መገናኛ ብዙኃንንም ጨምሮ ወጣቱ ስለ አያቶቹ ጀግንነት እንዲያውቅና ታሪኩን አውቆ በሥራው እንዲተገብረው በተደጋጋሚ መሰራት አለበት፡፡ በተጨማሪም «በአድዋና ሌሎች ታሪካዊ ክዋኔዎች ላይ የእምነት የራሳቸው ድርሻ ስለነበራቸው ወጣቱ ታሪኩን እንዲያውቅና ከማንነቱ ጋር እንዲያዋህድ አስተዋጽኦ ቢያደርጉ መልካም ነው» ይላል፡፡
የወጣቱ የአድዋ አደራ ዋነኛው የአንድነት ስሜቱን መጠበቅና የአድዋ ድል ጀግንነትና ስሜት እንዲቀጥል ማድረግ እንደሚገባው የሚናገረው ወጣት ኤርሚያስ ትውልዱ የአገሩን ሉዓላዊነትና አንድነት ለማስጠበቅ የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባም ያስገነዝባል፡፡ «ወጣቱ አንድነትን ሊረዳው የሚገባው የግድ አገርን ከውጭ ጠላት ለመከላከል ብቻ ሳይሆን በውስጥ ሰላም፣ በእርስበርስ አንድነትና ብዙ የጋራ ማንነቶች እንዳሉ አጉልቶ በማሳየት አንድ አገርን የመገንባትም አደራ አለበት» በማለት ተናግሯል፡፡
ወጣቱ ከአደዋ የተጣለበት አደራ አለበት በማለት ሃሳቡን ያካፈለን ሌላኛው ወጣት ደግሞ ቶላ ፈይሳ ነው፡፡ እንደ ወጣት ቶላ እምነት፤ አድዋን ጥበብ የተሞላበት የነፃነት የትግል ምልክት ተምሳሌት ነው፡፡ ይሁንና የአሁኑ ትውልድ ወጣት አያቶቹ በአድዋ የሰሩት ታሪክን ከማክበርና ከፍ ከፍ ከማድረግ ይልቅ መጠበቅም እየከበደው ነው፡፡ አያቶቹ መስዋዕትነት ከፍለው ያቆዩዋትን አገር ከመጠበቅ ይልቅም ልዩነቱን በማስፋት እርስ በርስ የሚያጋጩትን ጉዳዮች ይመርጣል፡፡
«አድዋ የኢትዮጵያ አንድነት መሠረት እንደሆነ መግባባት ሲገባ የብዙ ተቃራኒ ሃሳቦች መነሻና የሙግት አጀንዳ ሆኗል» የሚለው ወጣቱ ይህም የአባቶቹን የቀደመ ጀግንነትና ታሪክ በአግባቡ ካለመረዳት እንደሚመነጭ ይጠቁማል፡፡ አሁን ካለው የወጣቶች የሃሳብና የታሪክ መረዳት ልዩነትን የአድዋን ታሪክ በትክክለኛው መንገድ ማስረዳትና መግባባት መፍጠር እንደሚገባም ነው የሚመክረው፡፡
«የወጣቱ የታሪክ አረዳድ ሊስተካከል ይገባል» የሚለው ወጣት ቶላ፤ አድዋን እንዳለንበት ጊዜና ሁኔታ ሳይሆን እንደጊዜው መስዋዕትነትና እንደ ድሉ ዓላማ መረዳት ተገቢ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ለወጣቱ የአስተሳሰብ ልዩነት እየዳረገ ያለው ያልተመለሱ የታሪክና የማንነት ጥያቄዎች እንደሆኑና የአድዋ ድልን ከኢትዮጵያዊነት ጋር በማስተሳሰር መረዳትና አደራውንም በትክክል መወጣት እንደሚያስፈልግ ይናገራል፡፡
ወጣቶች ከአድዋ ድል ሊረዱና ሊወስዱ የሚገባው አደራ በጊዜው የአገር ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች የሕዝብ ኩርፊያ የነበረበትም ቢሆንም እንኳን ለአገር ጉዳይ ህብረ ብሔራዊነቱን ጠብቆ በአንድ ልብ መዝመቱን ነው፡፡ ወጣቱ ከአድዋ በአገር ጉዳይ ለመተባበር ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ሳይቀመጥ አንድ መሆንን፣ በጋራ መተባበርን የመረዳትና እነዚህንም የማስቀጠል አደራ እንዳለበትም ያስገነዝባል፡፡ «በርካታ ያልተማረ ኅብረተሰብ በነበረበት ዘመን ለአገር ጉዳይ በአንድነት ለጋራ ችግር አብሮ መተባበር ከቻለ አሁን ያለውም ትውልድ ያለውን እውቀት ተጠቅሞ የተሻለ ታሪክ ይሰራል» ይላል፡፡ ከድሉ ትምህርት በመውሰድ ዛሬ ወጣቱ የገጠመውን ችግር በአንድነት፣ በሃሳብ ክርክር በማዳበር አደራውን ሊወጣ እንደሚገባም ያመለክታል፡፡
ወጣት ቶላ በተደጋጋሚ «ወጣቱ የአድዋን ድል ድህነትን በማሸነፍ ሊደግም ይገባል» ከማለት ይልቅ መጀመሪያ ወጣቱ የአድዋን ድል በአግባቡ እንዲረዳ ማድረጉ ይቀድማል ባይ ነው፡፡ የአድዋን ምንነት ወጣቱ በአግባቡ እንዲረዳ ከተሰራ ለአገር ለውጥ እንዲነሳ ጥበብን፣ ጥንካሬን፣ ብርታትን በመውሰድ ለአገሩ እድገት እንዲሰራ ማድረግ እንደሚቻልም ያመለክታል፡፡ በቅድሚያ ግን ለወጣቱ ታሪኩን በአግባቡ መረዳትና መግባባት እንዲችል ማድረግ የሁሉም ዜጋ ግዴታ መሆኑን ይናገራል፡፡ ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ ክንዋኔዎች ወደ ትልቅ ደረጃ ለማሸጋገርም የአድዋን ድል መሠረት የሆነውን አንድነትን በቅድሚያ ወጣቱ ሊገነዘበው ይገባል የሚል እምነት አለው፡፡
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ስዩም በአድዋ ጦርነት ላይ መላ ኢትዮጵያዊ በመሳተፍና እንደ አንድ ሕዝብ ወደ ጦርነት የዘመተበትን ምክንያትን ወጣቶች ሊገባቸው እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡ በተለይ አባቶች አንድ ሆነው አንድ አገርን ለትውልዱ ለማቆየት መስዋዕትነት መክፈላቸውን ወጣቱ ልብ ሊለው የሚገባው ጉዳይ እንደሆነም ይገልፃል፡፡
«ብዙ ሺ አባቶች መስዋዕት ከፍለው ያቆዩለትን አንድ አገር ያሁኑ ወጣት አንድነት ጠብቆ ማቆየት ሊያቅተው አገይባም» በማለት ወጣቶች በስሜታዊነት አንድነትን የሚሸረሽሩ፣ እርስ በእርስ ጥላቻን የሚፈጥሩ አስተሳሰቦች በታሪክ ለነበረው የአንድነት ጉዞ እንደማይበጅ ከአድዋ ሊረዱ እንደሚገባ አቶ ቴዎድሮስ ያስገነዝባሉ፡፡
አቶ ቴዎድሮስ ወጣቱ ከአድዋ ሊማረው የሚገባው ሌላው ዋነኛ ጉዳይ የሚሉት ደግሞ በአድዋ ምክንያት ከሌላው አገራት በተለየ ኢትዮጵያ የነፃነት ሳይሆን የድል በዓል እንዲኖራት ማስቻሉን ነው፡፡ ይህንን እውነታ መነሻ በማድረግም አድዋ የወደፊት አብሮ በጋራ ለመኖር የሚያስችል በርካታ መልካም ነገሮች መነሻና አብሮነትን የሚያጎሉ ታሪካዊ አጋጣሚዎች ቁንጮ በመሆኑ ወጣቶች ቦታ ሊሰጡት እንደሚገባ ይጠቁማሉ፡፡
እንደ አቶ ቴዎድሮስ ገለፃ፤ ወጣቱ የአድዋ የተሰጠው አደራ በአድዋ የተከፈለውን መስዋዕትነት፣ ዓላማ፣ የድል ስሜቱንና ትርጉም በየትውልዱ ስሜቱን ጠብቆ እንዲሸጋገር የማድረግ ነው፡፡ ወጣቱ የአድዋ ድልን ዓላማ በመያዝ የበለጠ በአንድነት፣ በሰላምና በርካታ በጋራ በሚያስተሳስሩ ጉዳዮች በማጉላት ድህነትን ለመቅረፍ በአንድነት መስራት አለበት፡፡

ሰላማዊት ንጉሴ

Published in ማህበራዊ
Thursday, 01 March 2018 18:18

ዘረኝነት እንደ ስጋት

የሕዝቦቿ ተከባብሮና ተቻችሎ የመኖር ባህል ኢትዮጵያን በበርካታ የዓለም አገራት ዘንድ በአርአያነት እንድትጠቀስ አድርጓታል፡፡ በተለይም በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ያሏት መሆኗና እነዚህ ብሔር ብሔረሰቦች ደግሞ የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች ቢሆኑም ለዘመናት ተፈቃቅደውና ተቻችለው መኖራቸው ብዙዎችን የሚያስደምም እውነታ ነው፡፡ ይህም ፍቅራቸው ታዲያ ማንኛውንም የውጭ ወራሪ በመመከት የአገራቸውን ሉዓላዊነት አስጠብቀው እንዲኖሩ ያደረጋቸው መሆኑ እሙን ነው፡፡
ከምንም በላይ እርስ በርስ መከባበር፣ መረዳዳትና መተሳሰብ፣ ያለው ለሌለው እያካፈለ የመኖር ጉዳይ ዘር ቋንቋን ሳይለይ ዓመታትን የተሻገረ የአገሪቱ ሕዝቦች ብርቅዬ እሴት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚያም አልፎ አንዱ ከሌላው ጋር በመጋባትና በደም በመተሳሰሩ ይህን ሕዝብ መነጣጠል በምንም ዓይነት የማይደፈርና የማይቻል እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡
አሁን አሁን ግን ይህን ለዘመናት የቆየ ታላቅ እሴት የሚሸረሽሩ ግጭቶች እዚህም እዚያም ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ በተለይም አልፎ አልፎ ግጭቶቹ ዘርን መሠረት ማድረጋቸው አገሪቱን ወደማያባራ የእርስ በርስ ጦርነት እንዳይከታት ምሁራን ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡
አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው ምሁራን ዘረኝነት ራስን ከሌላው አስቀድሞ በማየት ልዩ ተጠቃሚ ለመሆን የሚደረግ ዝንባሌና ተግባር እንደሆነ ይስማማሉ፡፡ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ አቶ ካህሳይ ገብረየሱስ እንደሚናገሩት፤ ዘረኝነት መገለጫው ሰፊ ነው፡፡ በአሜሪካ በጥቁሮችና በነጮች መካከል የሚደረግ ሲሆን፤ በጀርመን ደግሞ በነጮች መካከል ባሉ ጎሳዎች የሚደረግ ሽኩቻና ራስን አጉልቶ ለማውጣት የሚደረግ ጥረት መሆኑ ታይቷል፡፡ በመሆኑም ለዘረኝነት ወጥ የሆነ ትርጉም መስጠት አዳጋች ነው፡፡
«ዘረኝነት የአንድ ማህበረሰብ ገዢ ፓርቲ ወይም ልሂቃን የዚያን ማህበረሰብ የበላይነት ለማረጋገጥና የራሳቸውን የፖለቲካ ሥልጣን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሀብት ቁጥጥር ለማረጋገጥ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው» ይላሉ፡፡ የተወሰኑ ቡድኖችን በማነሳሳት በሌሎች ላይ የሚደረግ የቀኝ አክራሪነት ዝንባሌ እንደሆነም ይጠቅሳሉ፡፡
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት ዶክተር ጫኔ ከበደም ዘረኝነትን በብዙ አግባብ ማየት እንደሚቻል ያብራራሉ፡፡ በተለይም ዘረኝነት በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የዘር ሐረግ የሚመዘዝለት የእገሌ ትውልድ እየተባለ በታሪክም በረጅም ጊዜ ተያይዞ የመጣ ዝንባሌ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
«ከቀደሙት መንግሥታት የዘረኝነት አስተሳሰብን በማጥበብ ረገድ አፄ ምኒልክን የሚያክል ታላቅ መሪ አልነበረም» የሚሉት ዶክተር ጫኔ፤ በተለይም የተለያዩ አመለካከት፥ ባህልና ቋንቋ ያላቸውን በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በማስተባበር አሁን ያለችውን ኢትዮጵያ በመፍጠር ረገድ ታላቅ መሪ እንደነበሩ ያነሳሉ፡፡ እንደ አድዋ ድል ያለ ታሪክን አጣቅሰውም በወቅቱ ጎልቶ የሚታይ የዘረኝነት ችግር እንዳልነበረ ያመለክታሉ፡፡ «እንዲያውም አንዱ ብሔረሰብ ሌላውን የሚናፍቅ በትና በእኩልነት የሚያይበት ጊዜ ነበር» ይላሉ፡፡ የአንድ ብሔር የበላይነት ችግርም እምብዛም እንደ ማይስተዋል ያመለክታሉ፡፡
በአንፃሩ ደግሞ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የአንድ ብሔርና ሃይማኖት የበላይነት ችግር ጎልቶ የወጣበት ወቅት እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ይህም ሲባል ግን በወቅቱ የነበረው ሥርዓት አማርኛን የሥራ ቋንቋ ከማድረግ ባለፈ የአማራን ሕዝብ ልዩ ተጠቃሚ አላደረገም ባይናቸው፡፡ «አማርኛ የሥራ ቋንቋ በመሆኑ ብቻ የአማራ ብሔረሰብ ራሱን ለይቶ በዘር በሌላው ላይ ተፅዕኖ የፈጠረበት ወቅት አልነበረም፡፡ ልክ እንደማንኛው የአገሪቱ ሕዝብ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ነበር እንጂ፡፡
አቶ ካህሳይ ግን «የዘረኝነት ችግር በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት እንዲያውም ጎልቶ ይታይ ነበር፡፡ በተለይም ንጉሡ ተበታትና የነበረችውን ኢትዮጵያ ወደአንድ አገር ለማምጣት ባደረጉት እንቅስቃሴ የአማራን የበላይነት አሳይተዋል» ሲሉ የዶክተር ጫኔን ሃሳብ ይቃወማሉ፡፡ አማራ በመሆኑ ብቻ ሌላውን ብሔረሰብ አስገድዶ ያስገብር እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡ ይህም ዘረኝነት ከአፄው ዙፋን ወርዶ በመኳንንቱና በሕዝቡም ዘንድ አልፎ አልፎ አልፎም ይታይ እንደነበር ማሳያ ነው ባይ ናቸው፡፡
«በእርግጥ እንደተባለው ችግሩ ጎልቶ የወጣው በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት መሆኑ የሚካድ ሃቅ አይደለም» ይላሉ አቶ ካህሳይ፡፡ በተለይም ደግሞ ንጉሡ ራሳቸው በገሃድ አንድ ቋንቋ አንድ ብሔር በማለት አውጀው ሌላውን የሚጨቁኑበት ሂደት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለሚነሳው የተዛባ ግንኙነት እርሾ እንደነበር ያመለክታሉ፡፡
ዶክተር ጫኔ «የደርግ ርዕዮተ ዓለም በራሱ ዘረኝነትን ይቃወማል» ብለው በጠቀሱት ሃሳብም አቶ ካህሳይ አይሰማሙም፡፡ መንግሥቱ ኃይለማርያም በራሱ አንደበት « የሰሜን ሸዋ ህዝብ ይዘምታል እንጂ አይዘመትበትም…» ብለው ነበር በማለት፤ ይህም ህዝብን ከህዝብ ለይቶ የማጋጨትና ከፋፍሎ የመግዛት ሁኔታም በስፋት ይስተዋል እንደነበር ምልክት ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡
«አፄ ሃይለስላሴ ለራሳቸው ካላቸው ንጉሳዊ ቤተሰብ ስሜት ጉዳዩን ወደ አማራ ወስዶ በማስጠጋት ብቻ 'አማራ ልዩ ተጠቃሚ ነው' የሚል ስያሜ ዛሬ ድረስ እንዲዘልቅ አድርገዋል» ይላሉ፡፡ እውነታው ግን ከዚያ ፈፅሞ የራቀ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ የተወሰነው የወታደሩ ክፍል በነፍጠኝነት ጠመንጃ አንግቶ ሌሎችን ግብር በማስገበር በወቅቱ ተፅእኖ ስለፈጠረ አማራው ልዩ ተጠቃሚ ነበር ማለት ታሪክን በቅጡ ካለማወቅ እንደሚመነጭ በመግለፅ፡፡
እንደ ዶክተር ጫኔ ማብራሪያ፤ በደርግ ዘመነ መንግሥት ደግሞ ጭራሽኑ የብሔረሰብ ማንነትን ርዕዮተ ዓለሙ በራሱ የማይፈቅድበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህም ሁኔታ ማንነታችን አልተከበረ ልንም የሚሉ የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱ ቡድኖች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ ከእነዚህም መካከል ትግራይን ነፃ የማውጣት ሃሳብ የሰነቀውን ህወሓትን የትጥቅ ትግል አብነት አድርገውም ሌሎችም ብሔር ተኮር እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡ ይህም ጥያቄ ሄዶ ሄዶ ሕገመንግሥታዊ ምላሽ ተሰጥቶት አገሪቱ ሁሉንም ማዕከል ያደረገ የፌዴራሊዝም ሥርዓትን ተግባራዊ አድርጋለች፡፡
የሕግ ባለሙያው አቶ ዝናቡ ይርጋ በበኩላ ቸው እንደሚሉት፤ መጠኑ ይለያይ እንጂ ሁሉም ሥርዓት ላይ የዘረኝነትና የአንድ ብሔር የበላይነት ችግር ተስተውሏል፡፡ በተለይም በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት ምንም እንኳን የአማራን ሕዝብ የሚገልፅና የአማራን ሕዝብ ለመጥቀም ተብሎ ተግባራዊ ባይደረግም መንግሥታትና ካድሬዎቹ ግን ተጠቅመውበታል፡፡ ለእያንዳንዱ ብሔር አብሮ ለመኖር የማያስችሉ ስያሜዎች እየተሰጡ የማግለል ሁኔታ ነበር፡፡ ይሁንና በሕዝቦች መካከል የሚፈጠር የዘረኝነት ችግር እምብዛም አልነበረም፡፡ ልክ እንዳሁኑ ሁሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ባለመዘርጋታቸው የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች ይበልጥ ለመቀራረብም ሆነ ለከፋ የእርስበርስ ግጭት የሚዳርጋቸው ዕድልም አልተፈጠረም፡፡
ጥቂት የማይባሉ ምሁራን አሁን እየጎላና ለግጭቶች መነሻ የሆነውን ችግር የፈጠረው የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ በተለይም አገሪቱ ከአሃዳዊ ሥርዓት ወጥታ በቀጥታ ሁሉም የራሱን ብሔር ባህልና ቋንቋ የሚያሳድግበት ሁኔታ ላይ መገባቷ የራሱ የሆነ ጥቅም ቢኖረውም ለራስ ብሔር አቀንቃኝነት ወይም ደግሞ ዘረኝነት መስፋፋት ሰበብ እንደሆነ ያነሳሉ፡፡
የፌዴራሊዝም ሥርዓት እንደ ኢትዮጵያ ላለች አገር ጠቃሚ ቢሆንም የክልሎች አወቃቀር ቋንቋንና ብሔርን ማዕከል ያደረገ በመሆኑ ከአገራዊ አንድነት ይልቅ ልዩነቶች እንዲሰፉ ማድረጉን ዶክተር ጫኔም ያምናሉ፡፡ በተለይም ደግሞ ባለፉት 26 ዓመታት ሕዝቦች ከአንድነታቸው ይልቅ ልዩነታቸው እየተነገራቸውና ልዩነታቸው እየተሰበከላቸው እንዲኖሩ በመደረጉ የራስን ብሔር ልዩ ተጠቃሚ ለማድረግ ዝንባሌ በሁሉም አካባቢዎች እንዲፈጠር ምክንያት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ይህም ዘረኝነት እንዲጸነስ ምክንያት ይሆናል፡፡
ይህም የቀደመው ተከባብሮና ተቻችሎ የመኖር ባህል እንዲጠፋ ዘረኝነት ጎልብቶ ወደ እርስበርስ ግጭት እንዲያመራ እያደረገው ነው የሚገኘው ባይ ናቸው፡፡ ይህም ደግሞ በልሂቃኑና በፖለቲከኛው ዘንድ ጎልቶ የሚታይ ችግር መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ «በአሁኑ ወቅት አገሪቱን ወዳልተፈለገና ወዳለመረጋገት የሚመራት አስተሳሰብ ብቅ ብቅ ያለው በዚሁ ተማርን በሚሉ ልሂቃንና ፖለቲከኞች የሚነዛው አስተሳሰብ ነው» ይላሉ፡፡ ባለፉት ዓመታት በሕዝቦች መካከል ቅራኔ የሚፈጥር የልዩነት ስብከቶች አሁን ላይ የደነደነ አቅም የፈጠሩ በመሆናቸው ከሕዝብ አዕምሮ ለማውጣት እንኳን አዳጋች ሆኗል፡፡
እንደአቶ ዝናቡ ማብራሪያ፤ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ መነሻው የብሔር ጭቆና የወለደው መሆኑ በራሱ ችግር አልነበረበትም፡፡ አገሪቱም ያላትን ብዝሃነት ማስተናገድ የምትችለው በዚሁ መንገድና ብቸኛው አመራጭ በመሆኑ በወቅቱ ወደዚህ ሥርዓት መገባቱ ተገቢ ነበር፡፡ ይሁንና የሕገመንግ ሥቱ መርሆች ተሸራርፈው ተግባራዊ ባለመደረ ጋቸው ሁሉም ብሔሩ የበላይ ተጠቃሚ እንዲሆንለት በሚያደርገው ሽኩቻ የዘረኝነት አደጋ እየተስፋፋ መጥቷል፡፡
ለዚህም አብነት አድርገው የሚጠቅሱት፤ በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠው መሠረት በክልሎች መካከል የሚነሳው የአስተዳደራዊ ወሰን አለመግባባት በወቅቱ አለመፈታቱን ነው፡፡ በትግራይና በአማራ እንዲሁም በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል ይነሱ የነበሩት ጥያቄዎች የማይሽር ጠባሳ ፈጥረው አልፈዋል፡፡ በሌሎችም አካባቢዎች የሚታዩና እዚህ እዚያም የእኔ ብሔር ማንነት አልተከበረም በሚል ሌላውን የመጥላት ዝንባሌ ተፈጥሯል፡፡ የዘረኝነት ችግር መነሻው አመራሩ እንደሆነ አቶ ዝናቡም ያምናሉ፡፡ አመራሩ የፌዴራሊዝምን ሳይንሳዊ ዳራ በሚገባ አልተገነዘበውም ይህም ጠባብነት እንዲጎ ለብትና የነበረውን ተቻችሎ የመኖር እሴት እንዲ ደበዝዝ ምክንያት እንደሆነም ነው ያብራሩት፡፡
አቶ ካህሳይ በበኩላቸው «ቀደም ሲል ዘረኝነት በባሰ መልኩ ችግር ይፈጥር እንደነበር እየታወቀ፤ የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የጋራ ውሳኔዎች መወሰን የሚያስችል ሕገመንግሥት በተረጋገጠበት ሁኔታ አሁን ዘረኝንት ተስፋፍቷል የሚባለው ነገር አልቀበለውም፡፡ ራስን አስተዳደር ስለተባለ ጥላቻ ሊያድርበት አይችልም» ይላሉ፡፡ ይህም የአንድነት ፍፁምነት አቀንቃኞች የነበራቸውን መሬት፣ ትጥቅና የፖለቲካ ሥልጣን በመነጠቃቸ ውና ያንን ለማስመለስ ሲሉ በሕዝቦች መካከል ቅራኔ ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት ውጤት እን ደሆነ ነው የሚያመለክቱት፡፡
የብዝሃነት ዴሞክራሲን ለመገንባት መሰራት ያለበት ስራ ባለመሰራቱ እንዲሁም ወጣቶችን ሕገመንግሥቱን እንዲያውቁት አለመደረጉ የአንድነት ፍፁምነት ያላቸው አክራሪዎች እየተደራጁ ሌሎችን እያታለሉ ወጣቱን ላልተፈለገ ሁኔታ እየገፋፉት መሆኑንና ይህም አሁን ለተፈጠረው ችግር ምክንያት እንደሆነ አቶ ካህሳይ ያብራራሉ፡፡
አገሪቱ አሁን ለገባችበት የፖለቲካ ቀውስ ዋነኛ ምክንያት የአንድ ብሔር የበላይነት መንገስ እንደሆነ፤ ሕዝቡ ለዓመታት የአንድ ብሔር በሁሉም መስክ ልዩ ተጠቃሚ የመሆን ዝንባሌ አለ በሚል እዚህም እዚያም ተቃውሞውን ማሰማት መጀመሩን ዶክተር ጫኔ ያምናሉ፡፡
በሌላ በኩልም የሀብት ተጠቃሚነትንና የሥልጣን ተጠቃሚነትን ለይቶ ያለማየት ችግር መፈጠሩን ይገልፃሉ፡፡ «በእኔ እምነት የሥልጣን ጉዳይ ሊሆን ይችላል ሀብት እያሳጣን ያለው፡፡ ለዚህም ነው የአገሪቱንም ሀብት እኩል መካፈል ያልቻልነው ሥልጣን ስላልተሰጠ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ የተደረሰው፡፡ ጥያቄው ግን በወቅቱ እየተፈታ ቢመጣ ኖሮ አሁን የሚታየውን ችግር ማስተናገድ አይገባንም ነበር» ይላሉ፡፡ ስለዚህ ውስጣዊ ችግራቸውን በዚያ መንገድ መረጋጋትን አለመፍጠሩና ተቻችሎ የመኖር እሴት በመሸርሸሩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ስጋት እየሆነ መጥቷል ባይ ናቸው፡፡
አቶ ዝናቡና አቶ ካህሳይ ግን የአንድ ብሔር የበላይነት አለ ብለው አያምኑም፡፡ ሁሉም ብሔር የራሱን አካባቢ እንዲያስተዳደር ዕድል ተሰጥቶት እያለና በራሱ ቋንቋ መናጋር እየቻለ የሌላ ብሔር ጣልቃ ገብነት ችግር አለ መባሉ እውነታን እንደማያሳይ ይገልፃሉ፡፡ አቶ ዝናቡ «አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ሁሉም ክልል ሉዓላዊ ነው፡፡ ማንም በማንም ላይ እጁን አንስቶ ጣልቃ መግባት አይችልም፤ እየገባም አይደለም» ይላሉ፡፡ ይሁንና አንዳንድ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ብሔረሰቦች ውክልናቸው ሙሉ ለሙሉ አለመረጋገጡን ያምናሉ፡፡ በተለይም ትላልቅ የመንግሥት ሥልጣኖች በአራቱ ክልሎች ብቻ መያዛቸው ለዘመናት ብዙዎችን የሚያስኮርፍ ጉዳይ መሆኑንም አልሸሸጉም፡፡
«የፌዴራል መንግሥቱን ያቋቋመው ደግሞ አብላጫ ድምፅ ያገኘው ፓርቲ ነው፡፡ አመራርም የሚሆነው የዚሁ ፓርቲ አባል ነው፡፡ ስለዚህ የብሔር የበላይነት መገለጫ ምንድነው?» በማለት መልሰው የሚጠይቁት ደግሞ አቶ ካህሳይ ናቸው፡፡ በዚህ ሳያበቁም «እውነቱን እንናገር ከተባለ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችን በአንድ ቋንቋ፥ በአንድ ሰንደቅ አላማ የሚገዛ ብሔር አለ ወይ? ኦሮሞው ትግርኛ ካልተናገርክ ተብሎ ተገዷል? የትኛው የትግራይ ተወላጅስ ነው አፋርን ወይም ኦሮሚያን የሚያስተዳድረው? ደግሞስ በአሁኑ ወቅት ትላልቅ የሚባሉ የመንግሥት ሥልጣኖችን የያዘው የአንድ ብሔር ተወላጅ ብቻ ነው? » ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
እንደ አቶ ካህሳይ እምነት፤ የአንድ ብሔር የበላይነት እንዳለ ተደርጎ የሚወራው በአንድነት ፍፁምነት አመላከከት ያላቸውና የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ ርዝራዦች አማካኝነት ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች የትግራይ ክልል ሕዝብ የብሔራዊ እኩልነት ጥያቄ አንስቶ ለብሔራዊ እኩልነት በትጥቅ የታገለ ለዚህ ሕገመንግሥት ተገቢውን መስዋት የከፈለ ሆኖ እያለ የበላይነትን ከትግራይ ሕዝብ ጋር የሚያገናኙት ትግራይን ካላዳከሙ አገሪቱን ዳግም መግዛት እንደማይችሉ በማመናቸው ነው፡፡ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መንግሥትንም ለማዳከምና ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር ለማጋጨት የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው፡፡ ይሁንና ይሄ ዘዴ በአሁኑ ወቅት ያለፈበት ከመሆኑም ባሻገር ሕዝቡም በዚህ የሚታለል አይደለም፡፡
እንደ አቶ ዝናቡ ማብራሪያ የአገሪቱ ሕዝብ አብሮ የመኖር እሴቶች እንዲጎለብቱ ማድረግ የሚቻለው ልክ መላው የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰብ በአድዋ ጦርነት ላይ ከውጭ የመጣውን ወራሪ በአንድነት እንደመከቱ ሁሉ አሁንም ያለውን ወጣት የአንድነትን ኃያልነት ማስተማር፤ ማስተባበር ሲቻል ነው፡፡ ያንን የቀደመ የአገር ፀጋ ለመመለስ ሁሉም በያለበት መስራት ይጠበቅበታል፡፡ በተለይም የመቻቻል እሴቶቻችን ለዓለም አርአያ ሆነው እንዲቀጥሉ ገዢው ፓርቲ የመሪነቱን ሚና ሊጫወት ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ የፌዴራሊዝም ፍልስፍናውና ሳይንሱን በአግባቡ ሊተገበርና በካድሬው ዘንድ ማስረፅ ቀዳሚ ሥራው መሆን አለበት፡፡
«ከጫፍ እስከ ጫፍ ተንቀሳቅሶ የመኖርና የመስራት መብት በሕገመንግሥቱ እውቅና መሰ ጠት ብቻ ሳይሆን በንብረቱ ላይ ዋስትና የማግኘት መብት ሊረጋገጥ ይገባዋል» የሚሉት አቶ ዝናቡ በደህንነት የመኖር ከወንድሞቹ ጋር እንደቀድሞው ፍቅሩን አጎልብቶ የመቀጠል፤ የእኔነት ስሜት እንዲያድርበት ማድረግ ያስፈል ጋል፡፡
አቶ ካህሳይም የአቶ ዝናቡን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ በተለይም የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ አተገባበር በሕገመንግሥቱ በተቀመጡ መርሆች አግባብ እንዲሆን የማድረጉ ሥራ በዋናነት የመንግሥት እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ሕገመንግሥቱን በአግባቡ የማሳወቁን ሥራ ከመንግሥት ካድሬዎች መጀመር እንደሚገባውም ያነሳሉ፡፡ ለወጣቱም በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ አካቶ ማስተማር ማስረፅ የመንግሥት የቤት ሥራ ነው ባይ ናቸው፡፡
እንደ ዶክተር ጫኔ ገለፃ፤ የዘረኝነትም ሆነ የእርስ በርስ ግጭቶች መነሻ የሚሆነው የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ እንደመሆኑ ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል፡፡ በተለይ ታች ወርዶ ሕዝቡን ማወያየት፥ በዘረኝነት አስተሳሰብ የታቃኘውን ካድሬም ማረቅ ከስህተቱ እንዲመለስ ማድረግ አለበት፡፡ ይህች አገር የተመሰረተችውና የቆየችው በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች አንድነትና መቻቻል እንደመሆኑ ይህ መልካም እሴት ከትውልድ ትው ልድ እንዲቀጥል ሁሉም ሕዝብ የበኩሉ መጫወት ይጠበቅበታል፡፡
«አሁን ያለው ሂደት በክልል ተንቀሳቅሶ የመኖር መብትን እየተገደበ ነው፡፡ በሌሎች አካባቢዎች ባፈራው ንብረት የመጠቀም ዕድሉም አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ ተለዋጭ ቋንቋ መቻል ልክ እንደ ወሬ አቀባይ መታየትና ለጥቃት የመዳረግ ሁኔታዎች እየፈጠረ ነው፡፡ መጨረሻ ላይ ተከላካይ አጥቂ ወደሚል ያመራና ወደ መንግሥት አልባ የማምራት ዕድሉ የከፋ ነው፡፡ ይህ ከቀጠለ ሥርዓት አልበኝነት የነገሰባትና ያልተረጋገች አገር ትፈጠራ ለች፡፡ የብዙ አገሮች ተሞክሮም የሚያሳየው ይሄው በመሆኑ» የሚለው ስጋት የአቶ ዝናቡ ነው፡፡
እነዚህ ሥራዎች ባይሰሩና አሁን ያለው የዘረኝነት ችግር እየተባባሰ ቢመጣ አገሪቱ ትበተናለች የሚል ድምዳሜ ዶክተር ጫኔ የላቸውም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ የሦስት ሺ ዓመት የመንግሥትነት ታሪክ ያስተናገደች አገር እንደመሆኗ አንደኛው መንግሥት በሌላኛው መንግሥት እየተገለበጠ አገሪቱ ግን ትቀጥላለች ባይ ናቸው፡፡ ሕዝቡን አንድነቱን አስጠብቆ የኖረ እንደመሆኑ የመገንጠልን ሃሳብ ፈፅሞ አይቀበለ ውም፡፡ ይሁንና የተጀመሩ ልማቶች በዚህ ችግር ምክንያት ሊጓተቱ ምንአልባት ሊቋረጡ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳላቸው አልሸሸጉም፡፡ ከአገራት ጋር ያለው የዲፕሎማሲ ሥራም ቢሆን አሉታዊ የሆነ ጥላ ሊያጠላበት እንደሚችል በመጠቆም፡፡

ማህሌት አብዱል

Published in ፖለቲካ

የባለሙያዎች የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ሥርዓት ለበርካታ ጊዜያት ቅሬታን ሲያስተናድ ቆይቷል፡፡ በተለይም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ስር የሚካተቱ የምህንድስናና የጤና እንዲሁም መሰል ሙያዎች ላይ የባለሙያዎች ምዝገባና የሙያ ብቃት ምዘና ሥርዓት በርካታ ጥያቄዎችን ሲያስነሳ እንደነበር ይታወቃል፡፡
እነዚህን ጥያቄዎች የሚመልስ ትክክለኛና ዓለም አቀፍ መስፈርት ያለው የባለሙያዎች ምዝገባና ብቃት ማረጋገጫ ሥርዓት ማምጣት እንደሚገባ ባለሙያዎች በተለያዩ ጊዜያት ሲመክሩም ቆይተዋል፡፡ በዚህም መሠረት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አሰባሳቢነት በችግሩ ላይ ባለሙያዎች ጥናት በማድረግ ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ ባለሙያዎቹ በጥናታቸው ባገኙት ውጤት መሠረት ያስቀመጡት ምክረ ሃሳብም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ምዝገባና ብቃት ማረጋገጫ በሦስተኛ አካል ይከናወን የሚል ነው፡፡
በጥናቱ ከተሳተፉ ባለሙያዎች መካከል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምህንድስና ትምህርት ክፍል የሲቪል ኢንጂነሪንግ መምህር የሆኑት ዶክተር አብርሃም አሰፋ፤ በኢትዮጵያ በሥራ ላይ ያለው የባለሙያ ምዝገባና ብቃት ማረጋገጫ ሥርዓት ምን እንደሚመስል ሰፋ ያለ ማብራሪያ ይሰጣሉ፡፡
እንደ ዶክተር አብርሃም ማብራሪያ፤ በኢትዮጵያ የባለሙያዎች ምዝገባና ብቃት ማረጋገጫ የሚሰጡት ሚኒስትር መስሪያ ቤቶችና ኤጀንሲዎች ናቸው፡፡ በእነዚህ ተቋማት የሚሰጠው የምዝገባና የብቃት ማረጋገጫ ሥርዓት በራሱ ዓለም አቀፍ መስፈርትን ያሟላል? በትክክል የሚመዝን ነው? ባለሙያዎች የሚያሳዩትን ተከታታይ ለውጥ ይፈትሻል? ሥነ ምግባርን ይመዝናል? በእያንዳንዱ ሙያ አሠራርን ተከታትሎ ፈትሾ ስህተት ሲፈፀም ተጠያቂ ያደርጋል? ባለሙያውንስ ያግዳል ወይ? የሚሉ ዋና ዋና ጥያቄዎችን የማይመልስ፤ በአጠቃላይ ሥርዓቱ ደካማ ነው፡፡
አሁን ያለው መመዘኛ ሥርዓት መሠረት ያደረገው የትምህርት ዝግጅት እና የሥራ ልምድ ነው፡፡ ልምድን እንደ ዋነኛ የሙያ መለኪያ ቢወሰድም፤ በኢትዮጵያ ያለው አሠራር የባለሙያ ብቃት ሲለካ የሥራ ልምድ በየትኛው ባለሙያ ስር ሰልጥኗል፣ ምን ያህል ክህሎት አግኝቷል፣ ምን ሰርቷል እና የሙያ ሥነ ምግባሩ ምን ይመስላል የሚሉትን ያላገናዘበ ነው፡፡
የባለሙያዎች ምዝገባ ያስፈለገው ባለሙያው እንዴት እየሰራ እንደሆነ ለመከታተል፣ ለመፈተሽና ስህተት ሲፈፀም ደግሞ ተጠያቂ በማድረግ እርምጃ ለመውሰድ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር አብርሃም፤ የኢትዮጵያ የሙያ ምዝገባ ሥርዓት ግን ባለሙያዎች አንዴ ከተመዘገቡ በኋላ ያለ ምንም ክትትል በተወሰነ ጊዜ ልዩነት ፈቃዳቸው የሚታደስበት አሠራር መኖሩን ይገልጻሉ፡፡ እንዲሁም የሙያ ብቃት ማረጋገጫውም ባለሙያዎች ራሳቸውን በየጊዜው እንዲያሻሽሉ፤ ከትምህርትና ከአዳዲስ ቴክኖሎጂ ግኝቶች እንዳይርቁ የሚያስገድድበት ሥርዓት እንደሌለም ያመለክታሉ፡፡
«በኢትዮጵያ ያለው የባለሙያ ምዝገባና ብቃት ማረጋገጫ ሥርዓት ትክክል አይደለም፡፡ የሙያ ምዝገባና የሙያ ማረጋገጫ ተቀላቅሏል፡፡ የሚመዘግበውም የሚመዝንና ብቃት የሚያረጋግጠውም አንድ ተቋም ነው» የሚሉት ዶክተር አብርሃም፤ ሁለቱን አሠራሮች መለየት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡ እንዲሁም ባለሙያን የሚመዘግብና ብቃት የሚያረጋግጠው አንድ ግለሰብ ከመሆኑ የተነሳም የምዘናው ጥራት ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ዶክተር አብርሃም ሲያስረዱም፤ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የዘርፉን ባለሙያዎች ይመዘግባል፤ ብቃትንም ይመዝናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ተቋሙ ጨረታ በማውጣት ፕጀክቶችን የሚያሰራውም፤ የተለያዩ የምህንድስና ፕሮጀክቶችን የሚመዝነውም ራሱ ተቋሙ ነው፡፡ ይህ አንድን ባለሙያ በሌላ በኩል እየቀጠሩ በሌላ በኩል ደግሞ የሙያ ሥነ ምግባርን አልጠበቀም እንደማለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በዘርፉ ያሉ ችግሮች ይበልጥ እየሰፉ መጥተዋል፡፡
«አሁን ያለው የሙያ ምዝገባና ብቃት ማረጋገጥ አሠራር እንደ ከፍተኛ የገንዘብ ምንጭ እየተቆጠረ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የባለሙያዎችን ትኩረት የሙያ ብቃት መሻሻል ላይ ሳይሆን፤ ገንዘብ ማግኘት ላይ ብቻ እንዲሆን አድርጓል» በማለት ይህንን እርስ በእርሱ የማይደጋገፍ አሠራር ለመቀየር ራሱን የቻለ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ከሙያው ጋር በጥቅም የማይገናኝ ባለሥልጣን እንደሚያስፈልግ ዶክተር አብርሃም ይጠቁማሉ፡፡ የሚቋቋመው ባለሥልጣን የሙያ ማህበራትን በማሳተፍ የምዘና ሥርዓቱን ዓለም አቀፍ ደረጃውንና አግባብነቱን በጠበቀ መንገድ እንዲሰራ ማቋቋም ተገቢ መሆኑንም ነው የሚያስረዱት፡፡
ባለሙያዎቹ ባቀረቡት ምክረ ሃሳብ እንደተመለ ከተው፤ አሁን አሁን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ጥራትና ሥነ ምግባር የጎደለው የሙያ አገልግሎት ተንሰራፍቶ ይገኛል፡፡ በጉድለቶች የተሞሉ የሙያ አገልግሎቶች መብዛታቸውን ማሳያውም በቂ አገልግሎት ሳይሰጡ የሚናዱ ሕንፃዎች፣ የሚፈርሱ መንገዶችና ድልድዮች እና የሕክምና ስህተቶች ናቸው፡፡ ጥራታቸውን ያልጠበቁ የሙያ አገልግሎቶችም ከጥንቃቄ እና ከሙያ ሥነ ምግባር መጓደል የተነሳ የሚከሰቱ ናቸው፡፡
ምንም እንኳን በተለያዩ የዘርፍ መስሪያ ቤቶች የተለያየ የብቃት ማረጋገጫ ሥርዓቶች ቢኖሩም፣ ማንኛውም የባለሙያ ምዝገባና ብቃት አረጋጋጭ አካል አገልግሎቱን ለመስጠት በአዋጅ ከመደገፍ ውጪ ሥልጣን በተሰጠው ሦስተኛ ወገን ዕውቅና ሊሰጠው (Accredited) መሆን እንደሚገባ ግንዛቤ ባለመኖሩና ሥራውም ያለምንም እውቅና እየተከናወነ ነው፡፡ ለባለሙያዎች ተከታታይ የሙያ ልማት (Continuous professional development)፣ የአገልግሎት ጥራትና ሥነ ምግባር ምዘናና ክትትል የሚደረግበት አሠራር የለም፡፡ ይህ አሠራርም ችግሮቹን ማቃለል አላስቻለም፡፡ ምህንድስና እና ህክምና በቀዳሚነት ይጠቀሱ እንጂ ሌሎች የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሙያዎች ውስጥ የሚታዩ የጥንቃቄ ጉድለቶች በማህበረሰብ ውስጥ የሚያስከትሉት ጉዳት ቀላል የሚባል እንዳልሆነና ለችግሮቹ መፍትሄው ትክክለኛ የባለሙያ ምዝገባና የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ሥርዓት መዘርጋት መሆኑን ያመለክታል፡፡
አሁን እየተሰራበት የሚገኘው የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ሥርዓት ላይ የታየው ጉድለትም በአንድ የሙያ ዘርፍ በተለያዩ የሙያ ብቃት አረጋጋጭ መስሪያ ቤቶች የተቀመጡ መስፈርቶች መለያየት፣ የአገልግሎቱ አመልካቾች በሚያስገቡት የትምህርትና የሥራ ልምድ ሰነድ ላይ ብቻ የተመሰረተ መሆኑንና የዓለም አቀፍ ተሞክሮን በበቂ ሁኔታ ያላገናዘበ በመሆኑ የተዘረጉት ሥርዓቶች ሊይዙ የሚገባውን መሠረታዊ ዓላማ የሳቱ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ለችግሩ መፍትሄ ካልተሰጠው ደግሞ መንግሥት ሊያከናውናቸው ያሰባቸው ትልልቅ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ከማሳደሩም በላይ የማህበረሰቡን ደህንነትና ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑንም ይጠቁማል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል መሐንዲሶች ማህበር ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አፈወርቅ ንጉሴ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የተሰጠው የባለሙያ ምዝገባና ብቃት ማረጋገጫ ሥርዓት መኖሩን ይናገራሉ፡፡ «ከዓለም አቀፉ የምዘና መስፈርት ጋር ሲተያይም በኢትዮጵያ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ የለም የሚያስብል ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሙያ ምዝገባና ምዘና ሥርዓት ኋላ ቀርና ደካማ ነው» በማለት በትክክል ባለሙያ የሚመዘገ ብበትና ብቃቱ የሚያረጋግጥ ሥርዓት እንደሌለ ያመለክ ታሉ፡፡
«ተቋማት ባለሙያ ማግኘት መቸገራቸውን፤ ባለሙያዎች ደግሞ ቀጣሪ ማግኘት እንዳልቻሉ በተደጋጋሚ ይናገራሉ፡፡ በዚህ ላይ ማህበራችን የምህንድስና ትምህርት ጥራትና የሥራ ቅጥር ዕድል ላይ ጥናት አድርጓል፡፡ በጥናቱ ያገኘነው ውጤት የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ሥርዓት አለመኖር ዋነኛው ችግር መሆኑን ነው» ይላሉ፡፡
የሙያ ብቃት ምዘና ሥርዓት በሚገባው ደረጃ አለመኖሩ በኢኮኖሚው ላይ እያስከተለ ያለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ኢንጂነር አፈወርቅ ይጠቁማሉ፡፡ እንደ እርሳቸው ማብራሪያ መንግሥት ከ60 በመቶ በላይ በጀት በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ላይ እያዋለ ቢሆንም እየወጣ ያለውን ገንዘብ ያህል ጥቅም እየተገኘ አይደለም፡፡ ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ፣ በጀት፣ በሚፈለገው ጥራት ደረጃ አለመጠናቀቅ እና ማገልገል ያለባቸውን ጊዜ ያህል አገልግሎት ያለመስጠታቸው ደግሞ የችግሩ ስር መስደድ ማሳያዎች ናቸው፡፡
የአገልግሎት ብቃት ሊሻሻል የሚችለው የባለሙ ያዎች የሥነ ምግባርና የሙያ ብቃትን በአግባቡ መመዘን ሲቻል መሆኑን ኢንጂነር አፈወርቅ ያስረዳሉ፡፡ አገሪቱ ለበርካታ ጊዜያት የተሸከመችው የሙያ ብቃት ምዘና ችግሮችን ለማቃለል ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የምዘና ሥርዓት መዘርጋት የግድ እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ፡፡
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ፤ አገራት እያደጉ ሲሄዱ የዕቃና የምርት ጥራት ብቻ ሳይሆን የባለሙያ ጥራትም የሚመዘንበትና የሚረጋገጥበት አሠራር የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
በተለይ የአገልግሎት ኢንዱስትሪ ሙያ ላይ ያተኮረ፣ የባለሙያውን ብቃት የሚጠይቅ እና በአገልግሎት ኢንዱስትሪው ቀዳሚ ተገልጋይ ሕዝብ በመሆኑ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ በራሱ መስፈርቱን የጠበቀ መሆን እንደሚገባው ነው የሚያብራሩት፡፡ በተለይ የአገልግሎት ዘርፉ የሕዝብን ጤና ከአደጋ የሚጠብቅ መሆን ሲገባው በኢትዮጵያ ግን ያለው የምዘና ሥርዓት ባለሙያዎች ብቃታቸውን ጠብቀው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንና አለመሆኑን የሚያረጋግጥ አለመሆኑን ይገልፃሉ፡፡
ኢንጂነር ጌታሁን በኢትዮጵያ እየተሰራበት ያለው የባለሙያ ምዘናና ብቃት ማረጋገጫ ሥርዓት ሂደት ላይ አለ የሚሉት ዋነኛ ክፍተት የሙያው ተጠቃሚ የሆኑ ተቋማት የምዘና አገልግሎቱን መስጠታቸው ነው፡፡ ይህ የምዘና ሥርዓት ደግሞ በሙያ ብቃት ምዘና ሥርዓት ላይ «ወንጀል» መሆኑን ነው የሚገልጹት፡፡ «ለምሳሌ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች ተጠቃሚ ተቋም ነው፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም የጤና ባለሙያዎች ተጠቃሚ ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት የባለሙያ ምዝገባና፣ ብቃት ማረጋገጥ ሥራን ይሰራሉ፡፡ ነገር ግን የሙያው ተጠቃሚ የሆነ ተቋም መመዘን አይችልም» በማለት፤ የባለሙያዎችን ምዝገባና ብቃት ማረጋገጥ ሥራውን የሚሰራው ከሙያው ጋር በጥቅም የማይገናኝ ሦስተኛ ወገን መሆን እንደሚገባ ነው የሚያስረዱት፡፡
በአገሪቱ በማንኛውም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሙያ ዘርፍ ሙያውንና ሥነ ምግባርን የሚመዝንና የሚያረጋግጥ ሥርዓት ባለመኖሩ ባለሙያዎች ጥፋት እያጠፉም በሞያው ውስጥ እንዲቆዩ ዕድል እየተሰጣቸው እንደሆነና ይህም የሙያ ሥነ ምግባር እንዲጓደልና ግዴለሽነት እንዲበረክት አድርጓል ባይ ናቸው፡፡
«በሲቪል ምህንድስና ሙያ ዲዛይኖችን የሚሰሩ ባለሙያዎች ልምዳቸው፣ ባህሪና ሥነ ምግባራቸው የተረጋገጠ አለመሆኑን ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ ተሰርተው በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚወድቁት ሕንፃዎችን የሚሰሩት ሙያቸው ተረጋግጧል በተባሉ ሙያተኞች ነው፡፡ ሙያተኞቹን አነስተኛ ቅጣት እየቀጡ ብቻ ማለፍ ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ነው፡፡ የሙያ ኢንዱስትሪው እየተመራ የሚገኘው በገንዘብ ነው፡፡ ገንዘብ ሙያን የሚያንቀሳቅስ ከሆነ ደግሞ እንደ አገር ችግር ውስጥ ነው ያለነው» በማለት፤ ገንዘብ የማስገኘት ዓላማ ብቻ የማይመራው የሙያ ምዘና ሥርዓት መፍጠር የችግሩ ቁልፍ መፍትሄ መሆኑን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ጌታሁን አሳስበዋል፡፡

ሰላማዊት ንጉሴ

Published in ኢኮኖሚ

ኢጣሊያ በመጪው መጋቢት ወር ብሔራዊ ምርጫ ታካሂዳለች፡፡ ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሙሉ ትኩረታቸውን ያደረጉትና የሕዝብን ድጋፍ ለማግኘት እየተሻሙ ያሉት ብንመረጥ በሕገወጥ ስደተኞች ላይ እጅግ ጠንካራ የሆነ እርምጃ እንወሰዳለን የሚል አጀንዳ በማራመድ ነው፡፡ የአፍሪካ ስደተኞች ከባድና በአደጋ የተሞላውን የሜዲትራንያን ባሕር ጉዞ በማቋረጥ ከሞት መትረፍ ከቻሉ የሚደርሱት ኢጣሊያ ጠረፎች ላይ ይሆናል፡፡ በርካታ ሕገወጥ ስደተኞች በባሕር ጉዞው በሚያጋጥማቸው አደጋ ይሞታሉ፡፡ ሰምጠው ይቀራሉ፡፡ አንዳንዴም አስከሬናቸው በፍለጋ ይገኛል፡፡ የሕገወጥ ስደተኞች ጉዳይ የኢጣሊያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥልጣን ላይ ለመውጣት በሕዝብ ፊት በሚያደርጉት ክርክር ድጋፍ ከሕዝቡ ለማግኘት የሚያስችላቸው ወሳኝ አጀንዳ ሆኖ ቀርቧል፡፡
በኢጣሊያ ብቻ ሳይሆን በአብዛኛው የአውሮፓ ሕብረት ሀገራት ይኸው የሕገወጥ ስደተኞች ጉዳይ ወሳኝ ሀገራዊ አጀንዳና ፖለቲካውን የሚዘውረው ጉዳይ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ሕገወጥ ስደተኞች ከተለያዩ ሀገራት ተነስተው ለሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ያለአቅማቸው ገንዘብ ከፍለው የሀገራትን ድንበር በስውር መንገድ መሪዎች አቆራርጠው ካለፉ በኋላ ነው ወደሚሳፈሩባቸው አነስተኛ መርከቦች የሚደርሱት፡፡
መርከቦቹ ከአቅማቸው በላይ በሰው ላይ ሰው ደራርበው ስለሚጭኑ ባሕር ላይ የመስጠምና የመገልበጥ አደጋ ያጋጥማቸዋል፡፡ ሰዎች በብዛት ይሞታሉ፡፡ በባሕር ውስጥ አውሬዎች ይበላሉ ወይንም አስከሬናቸው ይጠፋል፡፡ ቢገኝም ማንነታቸው ላይለይ ይችላል፡፡ የተሻለ ኑሮና ሕይወት ፍለጋ በሕገወጥ መንገድ ወደ አውሮፓ የሚደረገው ስደት ከሞት ጋር ፊት ለፊት በመጋፈጥ የሚደረግ ጉዞ ነው፡፡ ሞትን በእርግጠኝነት እያዩት ወሰደኝ አልወሰደኝ በሚል ትንቅንቅ የሚደረግ የሥቃይ የፈተና የመከራ ጉዞ፡፡
ይህም ሆኖ ኢጣሊያ ወደብ መድረስ የቻሉትን ለመቀበል ሌላ ፈተና ነው፡፡ በዚህ መልኩ ከአፍሪካ ተነስተው የሚጓዙት ሕገወጥ ስደተኞች በተለያዩ ዓመታት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩት ሕይወታቸው አልፏል፡፡
ኢጣሊያም ሆነች የአውሮፓ ሕብረት ሀገራት በሕገወጥ ስደተኞች ተጨናንቀዋል፡፡ የየሀገሩ ሕዝብ ሕገወጥ ስደተኞችን ማስወጣትና ወደመጡበት መመለስ ይፈልጋል፡፡ በስደተኞቹ ወደሀገራቸው መግባትና መኖር ምክንያት የሀገሬው ነዋሪ ፍርሀት ይሰማዋል፡፡ ለስደተኞችም ጥላቻ አለው፡፡ ይህ ለኢጣሊያም ሆነ ለአውሮፓ ሕብረት ሀገራት መንግሥታት እጅግ አስጨናቂ ሁኔታዎችን ፈጥሯል፡፡ ፖለቲካቸውንም እየለወጠው ይገኛል፡፡
የቢቢሲዋ ወርልድ ቱ ናይት ዘጋቢ የሆነችው ሪቱላ ሻህ ከሚላን ኢጣሊያ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ ከፋሽዝም ነፃ የወጣችበትን በዓል ስታከብር ታድማ የታዘበችውን በተመለከተ እንዳሰፈረችው፤ ካሳ ፓውንድ የተባለው ፓርቲ ክንፍ አባል የሆነ ማሲሞ ትሬፍሌቲ በኩራት መንፈስ ተሞልቶ እሱና ፓርቲው ፋሽስት መሆናቸውን ይናገራል፡፡ ለወደፊቱ ኢጣሊያ ፊቷን በአውሮፓ ሕብረት ላይ እንድታዞር ድንበሮቿን እንድትዘጋ ስደተኞችን በሙሉ ወደ ሀገራቸው እንድትመልስ ይፈልጋል፡፡
ካሳ ፓውንድ የተባለው ፓርቲ በጣም አነስተኛ በሆኑ ኢጣሊያውያን የሚደገፍ ነው፡፡ ሆኖም ግን ብሔርተኝነቱና ፀረ ስደተኞች የሆነው አቋምና ውንጀላው በመጋቢት 4 በሚካሄደው አጠቃላይ ብሔራዊ ምርጫ በሚሳተፉት ሌሎች ፓርቲዎችም በመስተጋባት ላይ ይገኛል፡፡
ባለፉት አራት ዓመታት ወደ 600 ሺ የሚደርሱ ሰዎች እጅግ አደገኛ ጉዞ በማድረግና ሜዲትራንያን ባሕርን በማቋረጥ ኢጣሊያ ወደቦች ደርሰዋል፡፡ አሁን በኢጣሊያ የሚገኙ ሁሉም ዓይነት ፖለቲከኞች በዚህ አዲስና እየጨመረ በመጣው ያልተፈለጉ ደራሾች ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስዱ ለማሳየት የስደተኞችን ጉዳይ ወሳኝ አጀንዳ አድርገው በመወዳደር ላይ ይገኛሉ፡፡
የተሰበሰቡት የሕዝብ አስተያየቶች የሚታመኑ ከሆነ በጥንቃቄ ነው መታየት ያለባቸው፡፡ የኢጣሊያ ምርጫ የሚካሄደው በአዲስ የድምጽ አሰጣጥ ሥርዓት ሲሆን በሲሊቪዮ ቤርሎስኮኒ የሚመራው የማዕከላዊ ቀኝ ጥምረቱ ፎርዛ ኢጣሊያ እየመራ ነው፡፡
ሚስተር ቤርሎስኮኒ በኢጣሊያ የሚኖሩትን ሕገወጥ ስደተኞች ግዙፍ በሆነ ደረጃ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እንደሚያደርጉም ቃል ገብተዋል፡፡ የሰሜን ሊግ በመባል የሚታወቀው የጥምረቱ አንዱ ዋነኛ አባል ነው፡፡ መሪው ማቲዮ ሳልቪኒ የፈረንሳይ ቀኝ አክራሪ ተቃዋሚ መሪ የሆነው ማሪን ሌፔን ጓደኛና የሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን አድናቂ ነው፡፡ መፈክሩ ኢጣሊያ ፈርስት (ኢጣሊያ ትቅደም) የሚል ነው፡፡
ግሪሞልዲ የሊጉ ምክትል ኃላፊ ሲሆን በፓርላማ ዳግም ለመግባት እየተወዳደረ ይገኛል፡፡ በሲጋራ በታፈነው ቢሮው ኢጣሊያ ማን እዚህ መምጣትና መኖር እንዳለበት መምረጥ መቻል አለባት ሲል ነግሮኛል በማለት የቢቢሲ ዘጋቢዋ ገልጻለች፡፡ ስደተኞችን ከዩክሬን ወይም ቤላሩስ መውሰድ የተመረጠ ነው፡፡ ሙስሊሞች አይ ደሉም፡፡ አሸባሪዎች ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ምርጫ ለማድረግ መብት እንዲኖረኝ እፈል ጋለሁ፡፡ እኔ እንደማስበው በዚህ ሰዓት ስደተኞችን አንፈልግም ሲል እንደገለጸላት ጋዜጠኛዋ ጠቅሳ ለች፡፡
ሚስተር ግሪሞልዲ ጠረፍ ለማቋረጥና ወደ ኢጣሊያ ለመግባት የሚሞክሩትን ሕገወጥ ስደተኞች መልሰው ወደ ኢጣሊያ የሚልኩትን የፈረንሳይና የአውስትራሊያ ፖሊሶች ጥረት ይደግፋሉ፡፡ መንግሥታችን ሕገወጥ ስደተኞችን መውሰድ ይመርጣል፡፡ ፈረንሳይ ጠረፉን የምትቆጣጠርበት ምክንያት ይሄ ነው፡፡ አውሮፕላን ከለንደን ወደ ሞስኮ ወይም ወደ አንካራ ብትይዝ ዶክመንትህን እንድታሳያቸው ይጠይቁሀል፡፡ ይሄ መደበኛ አሠራር ነው ብዬ አምናለሁ ብለዋል ግሪሞልዲ፡፡
ከሚላን የ20 ደቂቃ ጉዞ በማድረግ የስደተኞችን ሁኔታ የታዘበችው ዘጋቢዋ ታዳጊ የሆኑ የወንድ ልጆች የጠረጴዛ ቴኒስ ሲጫወቱ አግኝታቸዋለች፡፡ ስደተኞች ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ኢጣሊያ የደረሱት ያለ ሸኚ ነው፡፡
ጃዋድ አስራ ሰባት ዓመቱ ነው፡፡ ቤተሰቡ የሚገኘው ሞሮኮ ውስጥ ነው፡፡ ማስቲካውን እያላመጠ በስሜታዊነት ተውጦ እንዴት ብቻውን ወደ ኢጣሊያ እንደመጣ ይገልጻል፡፡ የተሻለ ሕይወትና ኑሮ ይፈልጋል፡፡ ለስደተኞች ተቃራኒ የሆነው የኢጣሊያ ሕዝብ ባለው የማገድ ሀሳብ አይስማማም፡፡ እዚህ ጥቂት ሰዎች ለውጭ ዜጎች ጥላቻና ፍርሀት እንዳላቸው አውቃለሁ፡፡ አንዳንዶች ብዝሀነት ለኢጣሊያ ጥሩ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ እንደ አደጋ ነው የሚያዩን፡፡ ሰዎች የሚያስቡበትን መንገድ መለወጥ አልችልም ብሏል፡፡
አቋማቸው ሲመዘን ዋነኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምርጫው ተፎካካሪ የሆኑት አብዛኛዎቹ ኢጣሊያውያን ስደተኞች አደጋ ናቸው ብለው እንደሚያምኑ ይገልጻሉ፡፡ የሕዝብ አስተያየት መስጫዎች እንደሚገልጹት በቅርብ የተመሰረተው የአምስት ኮከብ ንቅናቄ (ፋይፍ ስታር ሙቭመንት) በድምጽ ሰጪዎች ውስጥ ብቸኛው እጅግ ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ ያለው ፓርቲ ነው፡፡ በአውሮፓ ላይ ጥርጣሬ ያለውና በስደተኞች ጉዳይ ጠንካራ አቋም በመያዝ የሚኮንነው የአውሮፓ ሕብረትን ነው፡፡ የፓርቲው ምክትል ኃላፊ ማንሊዮ ዲ ስቲፋኖ እዚህ የመጡት በትክክለኛው መንገድ መዋሀድ አለባቸው፡፡ ገንዘብ የምንወስደው የአውሮፓ ሕብረት ክፍት ወደብ ለመሆን ነው፡፡ ያ ደግሞ አግባብ አይደለም ብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢጣሊያ ጠረፎች የሚደርሱት ሰዎች ቁጥር በሚገርም ሁኔታ ቀንሷል፡፡ ይህም በከፊል በኢጣሊያ በሚመራው የአውሮፓ ፖሊሲ አማካኝነት ነው፡፡ የሊቢያን ባለሥልጣናት በመርዳት ሜዲትራንያን ባሕርን ለማቋረጥ የሚሞክሩትን በመያዝና ወደ ሊቢያ የእስርቤት ማዕከሎች እንዲመለሱ በማድረግ ነው ቁጥሩን መቀነስ የቻሉት፡፡ ፖሊሲው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢሰብአዊነት ተወቅሷል፡፡
ይህ የተደረገው አሁን በሥልጣን ላይ ባለው በግራ ማዕከላዊ ዴሞክራቲክ ፓርቲ በሚመራው መንግሥት ነው፡፡ ሆኖም ግን ሊያ ኩዋርታፔሌ የፓርቲው ምክትል ኃላፊ አሁን እየተከተሉት ያለውን አሠራር ምርጥ መፍትሄ ነው ይላሉ፡፡ አያይዘውም የሊቢያ ባለሥልጣናት ጠረፋቸውን ነቅተው እንዲጠብቁ መጠየቅ ሕገወጥ ፍሰትንና ሕገወጥ አዘዋዋሪዎችን ማስቆሚያ መንገድ ነው ብለዋል፡፡
የእርዳታ ሠራተኞችና ዓለም አቀፍ ሪፖርተሮች ብቻ በስምምነቱ መሠረት ሁኔታዎቹን መመርመር ማጣራት እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በሥልጣን ላይ እንዳለ መንግሥት የፓርቲው ፈተና የቀኝ ክንፍ ፓርቲዎችን ከባድ የሆነ ፀረ ስደተኛ አሳማኝ ንግግር መቀላቀል ወይንም አለመቀበል ነው ብለዋል፡፡ የምርጫውን ውጤት ለመተንበይ አይቻልም፡፡ እውነት የሆነው ነገር በኢጣሊያና በአብዛኛው የአውሮፓ ሕብረት ሀገራት ፖለቲካው እንደገና መልክ እየያዘ ያለው በስደተኞች ጉዳይ መሆኑ ነው።

ወንድወሰን መኮንን

Published in ዓለም አቀፍ

በየትኛውም ዓለም ሀገራት የሚመሩባቸው የራሳቸው ሕግና ሥርዓት ይኖራቸዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የሚከተሉ መንግሥታት ወደ ሥልጣን ለመምጣትም ሆነ ከሥልጣን ለመውረድ የሕዝቡን ይሁንታ ይፈልጋሉ፡፡ ሕዝቡ ደግሞ በየደረጃው ያሉትን መሪዎቹን ለመምረጥ የሚያቀርቡትን ሃሳብ ይመዝናል፡፡ በመጨረሻም በገቡት ቃል መሠረት ያስቀመጡትን ሃሳብ በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ ካልቻሉ ዴሞክራሲያዊ መብቱን ተጠቅሞ ከሥጣልን ሊያባርራቸው ይችላል፡፡
ይህ ሕግ በአገራችንም ዋነኛ የሥልጣን መወጣጫና መውረጃ መስፈርት ሆኖ ማገልገል ከጀመረ 23 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት ተግባራዊ ከሆነ ጀምሮ ምርጫን መሠረት በማድረግ ወደ ሥልጣን ላይ የሚወጣበትና በምርጫ ሥልጣን የሚለቀቅበትን ሥርዓት በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ በሥልጣን ላይ ያሉ አካላትም ለመረጣቸው ሕዝብ ግልፀኝነትን መፍጠር ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት በየደረጃው ባለው የመንግሥት መዋቅር ከእቅድ ዝግጅት ጀምሮ ኅብረተሰቡን የማሳተፍና አብሮ የመስራት ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡ በሌላ በኩል በመንፈቅ ወይም በዓመታዊ አፈፃፀም ደግሞ አጠቃላይ ከእቅዱ አንጻር የተከናወኑ ሥራዎችን ሪፖርት ለኅብረተሰቡ የማቅረብና የማስተቸት ሥራዎችም በተለያዩ ተቋማት ሲከናወኑ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ የሕዝብ ክንፍ ተብለው በኅብረተሰቡ የተወከሉ አካላትም አፈፃፀሙን የሚከታተሉና የሚገመግሙ ሲሆን፤ አስፈጻሚ አካላት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ያግዛል፡፡ ይህ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገለጫ በመሆኑ የሚበረታታ ጉዳይ ነው፡፡
በአንፃሩ ግን በአገራችን ከእቅድና ከሪፖርት ጋር በተያያዘ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን የተለያዩ አካላት ሲገልጹ ይሰማል፡፡ በትክክልም በተለያዩ ተቋማት የሚቀርቡ የአፈጻፀም ሪፖርቶች በተጨባጭ መሬት ላይ የሚታየውን ነባራዊ ሁኔታ የዳሰሱ ናቸው ወይ ብለን ስንጠይቅም የምናገኘው መልስ ከዚህ በራቀ መልኩ የተጋነነ ሊሆን ይችላል፡፡ ባለፈው ወር መጨረሻ አካባቢ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአንዳንድ ተቋማት የሚቀርበውን የሃሰት ሪፖርት ለመከላከል አሃዛዊ መረጃዎችን የሚያሰባስብ ኤጀንሲ እንደሚቋቋም የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማስታወቃቸውም ችግሩ ምን ያህል እየከፋ መምጣቱን አመላካች ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ በትግራይ የተጀመረው ችግሩን የመከላከል እቅድ በራሱ ጥሩ ነገር ቢሆንም ውሸታሞችን እስከመቼ ጠብቆ መስራት ይቻላል የሚለው ግን ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ይህ ችግር ደግሞ የመላ አገሪቱ ችግር እንደመሆኑ በሌሎች ክልሎችና ተቋማትስ ዘላቂው መፍትሄው ምንድነው የሚለው ጉዳይ ሊተኮርበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
በሀገራችን ከእቅድና ሪፖርት ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮች በርካታ ናቸው፡፡ ከእቅዱ ስንጀምር በርካታ ተቋማት ዓመታዊ እቅዶቻቸውን ሲያዘጋጁ የጥራት መጓደል ችግር ይታይባቸዋል፡፡ አብዛኞቹ እቅዶች (አንዳንድ በጥራት የሚያዘጋጁ እንዳሉ ታሳቢ መደረግ አለበት) ተቋሙ ያለውን የማስፈፀም አቅም ከግምት ያስገባ አይደለም፡፡ በዚህ የተነሳ እቅዶቹ ሲዘጋጁ የሚያየውን አካል ለማስደሰት ወይም ይህችን ብቻ ነው እንዴ የምታቅደው እንዳይባል ብቻ ተለጥጠው ይቀመጣሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዶቹ ሆን ብለው ከእቅድ በታች የሚያቅዱም አሉ፡፡ የእነዚህ ሁለት አካላት ፍላጎት የተለያየ ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ የማይችሉትን የተለጠጠ ዕቅድ በማስቀመጥ ያልተገባ ቃል በመግባት ሕዝቡን ለመሸንገል ታስቦ የሚዘጋጅ ነው፡፡ ለምሳሌ በቀጣዩ በጀት ዓመት በዚህ አካባቢ እንዲህ ዓይነት መሠረተ ልማቶችን እገነባለሁ፤ እንዲህ ዓይነት ችግሮችን እቀርፋለሁ፣ ይህንን አደርጋለሁ፤ ወዘተ እየተባለ ኅብረተሰቡ ተስፋ ይዞ እንዲቀመጥ የማድረግ ስልት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የመሠረት ድንጋይ እስከ ማስቀመጥ የሚደርስ ቃል መግባትን ያካትታል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በወረቀት ላይ የሚሰፍሩ እቅዶችን ከአቅም በታች ማድረግ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ አፈጻፀማቸውን ከመቶ በላይ ለማድረግና ራሳቸውን ለመኮፈስ የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር አንዳንድ ጊዜ እስከ ከ100 በላይ እቅድ አፈጻፀም የሚያሳዩ ነገር ግን ለኅብረተሰቡ ምንም ጠብ የሚል የረባ ነገር ሳያሳዩ ዓመቱ የሚያልቅባቸው ተቋማት ራሳቸውን ቢያዩ መልካም ይሆናል፡፡
በቅርቡ በደቡብ ክልል ወልቂጤ አካባቢ ከዓመታት በፊት የመሠረት ድንጋይ የተጣለበት የሆስፒታል ግንባታ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ባለማሳየቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ያላቸውን ቅሬታ በተቃውሞ ማሰማታቸው ይታወሳል፡፡ ይህ ጥያቄ ምን ያህል ኅብረተሰቡ እያንዳንዱን ጉዳይ በጥልቀት እየገመገመ መሄድ መጀመሩን ማሳያ ነው፡፡ የኅብረተሰቡ ግንዛቤ እያደገ በሄደ ቁጥር የሃሰት ሪፖርት ወይም ኅብረተሰቡን ለመሸንገል የሚደረጉ ማናቸውም ጥረቶች ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ያመዝናል፡፡ በወልቂጤ አካባቢ የተነሳው ቅሬታ መነሻ ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት ችግሮች በየቦታው መኖራቸው እሙን ነው፡፡ የመሠረት ድንጋዮቻቸው ተጥሎ የሚረሱ በርካታ ሥራዎች በየቦታው አሉ፡፡ እነዚህ ሥራዎች በመጀመሪያ ታቅደው ከተጀመሩ በኋላ የሚቆሙት በእቅድ ባለመመራታችን መሆኑን መገንዘብ ይገባል።
በሌላ በኩል በመዲናችን አዲስ አበባ በርካታ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ አሁንም እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ ከእነዚህ መካከል ደግሞ በየቦታው የሚካሄዱ የመልሶ ማልማት ሥራዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ በዚህ ዘርፍ ከተማዋን አፍርሶ የመገንባት ያህል በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን ሥራዎቹ በወቅቱ ወደ ተግባር የማይገቡበትና መልሰው የኅብረተሰቡ የቅሬታ ምንጭ የሚሆኑበት አጋጣሚም ቀላል አይደለም፡፡
ለአብነት በከተማዋ በልደታ ክፍለ ከተማ የሱማሌ ተራ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ያለው የመልሶ መልማት ሥራ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች ከሁለት ዓመታት በፊት ከሚኖሩበት እና ከሚሰሩበት አካባቢ ሲነሱ ትንሽ ጊዜ ይሰጠን የሚል ቅሬታ ያነሱ ነበር፡፡ በወቅቱ ግን ሰሚ አላገኙም፡፡ በክረምት ምክንያትም በርካቶች ለችግር ተጋልጠዋል፡፡ ነገር ግን ይህን አካባቢ መልሶ የማልማቱ ሥራ ለማፍረስ የተቸኮለውን ያህል ሊፈጥን አልነበረም፡፡ ይህ ደግሞ ከእቅድ ጋር ተያይዞ ያለ ችግር ካልሆነ ምን ሊባል ይችላል?
ለመሆኑ ከዚህ አንፃር አንድ ሥራ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ የማይሰራው ለምድን ነው? በዚህ አካባቢ የልማት ሥራ ይከናወናል ተብሎ እቅድ ከተያዘና ነዋሪዎች ከቦታቸው ከተነሱ በኋላ በወቅቱ ወደ ሥራ የማይገቡበት ምክንያትስ ምንድነው? ይህ በቅርበት ተፈትሾ እያንዳንዱ አካል በእቅዱ መሠረት እንዲሰራ ካልተደረገና የተጠያቂነት ሥርዓት ካልተበጀ የመልካም አስተዳደር ችግር መንስኤ መሆኑ አይቀርም፡፡ እንዲህ ዓይነት እየተጀመሩ ሳይከናወኑ የሚቆዩ ፕሮጀክቶች ወረድ ተብሎ ችግራቸው ቢፈተሽ በየዓመቱ ይህንን እሰራለሁ እየተባለ ከሚቀመጥ የተጋነነ እቅድና በዓመቱ መጨረሻም ላልተሰራው ሥራ የሚቀርቡ የውሸት ሪፖርቶች ናቸው፡፡
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በአንድ አካባቢ የተሰሩ መልካም ተግባራት ሲኖሩ እነዚህን ተሞክሮዎች ወስዶ ከመተግበር ይልቅ ባለቤት ለመሆን የሚደረጉ ሩጫዎችም አሉ፡፡ በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ የሥራ ዕድል ፈጠራን በተመለከተ አጠቃላይ መረጃ ፈልጌ ጉዳዩ የሚመለከተውን አካል ስፈልግ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ቢሮ እንደሆነ ተነግሮኝ ወደዚያው አመራሁ፡፡ ቢሮው በእርግጥም ስለጉዳዩ የሚመለከተው ቢሆንም በወቅቱ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮም ኃላፊነት እንዳለበት ተነግሮኝ ወደዚያም አመራሁ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮም በተለይ ከስደት የተመለሱትን ሴቶች በመለየት እንደሚያደራጅ ተገለፀልኝና ከእነዚህ አካላት መረጃ ለማግኘት አመራሁ፡፡ የሚገርመው ነገር በእነዚህ ሦስት አካላት ያለው ሪፖርት የተለያዩ ከመሆኑም ባሻገር አንዱ ከሌላው ጋር የሚናበብ አለመሆኑ ነው፡፡ ሁሉም በየራሳቸው መንገድ በሚመቻቸው ሁኔታ ያጠናቀሩት ሪፖርት እንጂ በተጨባጭ መሬት ላይ ያለውን እውነታ የሚያሳይ አልነበረም፡፡
በአንድ ወቅት ችግኝ መትከል የበርካታ ተቋማት መደበኛ ሥራ እስከሚሆን ድረስ መረባረብ እንደልምድ የተወሰደበትና ይህም የጠንካራ አመራር መገለጫ ተደርጎ የሚታይበት ጊዜ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ታዲያ ከዚህ ጋር ተያይዞ በየቦታው ተተከሉ ተብሎ ሪፖርት የሚደረገው ችግኝ በትክክል ተግባራዊ የተደረገ ቢሆን ሀገሪቷ የአማዞን ጥቅጥቅ ጫካ ትሆን እንደነበር አንዳንድ ሰዎች በምፀት ያነሳሉ፡፡
ከጤና ኤክስቴንሽን ጋር በተያያዘም በአንድ ወቅት ሲነገሩ የነበሩ ሪፖርቶች ግነት የታከለባቸው እንደነበሩ ብዙ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ እውን የጤና ኤክስቴንሽን ሥራው ሪፖርት የሚደረገውን ያህል ነውን? ይህ እውን ቢሆን በዚህች አገር የጤና ችግር አይኖርም ነበር፡፡
የእርሻ ጊዜ በደረሰ ቁጥር በገበሬው ከሚፈለጉ አቅርቦቶች ውስጥ ማዳበሪያ አንዱ ነው፡፡ በተለይ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የማዳበሪያ ስርጭትና አጠቃቀም ጠቃሚ መሆኑን የተገነዘበው መንግሥት ገበሬው በማዳበሪያ እንዲጠቀምና ምርቱን እንዲያሳድግ ይሰራል፡፡ ለዚህ ደግሞ በየደረጃው ያሉ የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የግብርና ባለሙያዎች እንዲሁም በየደረጃው ያሉ አመራሮች ኃላፊነት ወስደው ይሰራሉ፡፡
ከዚህ አንጻር ግን በማዳበሪያ ይጠቀማል ተብሎ ሪፖርት የሚደረገውና ለገበሬው ደርሷል እየተባለ ሪፖርት የሚደረገው የማዳበሪያ መጠን መሬት ላይ ካለው እውነታ በፍፁም የተራራቀ በመሆኑ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት እንቅፋት ሆኗል፡፡
በአንድ ወቅት በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የሚሰሩ የልማት ሥራዎችን ለመጎብኘትና ፕሮግራም ለመስራት ወደ አንድ የአገራችን አካባቢ ተጉዘን ነበር፡፡ በወቅቱ በቦታው ላይ ስንደርስ በአንዲት መንደር በኅብረተሰቡ ተሳትፎ የተሰራው ሥራ የሚገርምና እጅግ የሚያበረታታ ነበር፡፡ እናም ይህን በማየት ሌሎችንም በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ለማወቅ ፈልገን የአካባቢውን የወረዳ አመራሮች ስንጠይቅ ሌላ ቦታ ለመሄድ ወቅቱ ምቹ ባለመሆኑ ሌላ ጊዜ ብትመጡ ይሻላል የሚል ምላሽ ሰጡን፡፡ በኋላ ቆይተን ስናጣራ ግን ሌሎቹ አካባቢዎች ፈፅሞ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ያልነበረባቸው መሆናቸውን ተገነዘብን፡፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ ሪፖርቱ በሁሉም ወረዳዎች የተሰራው ሥራ ስኬታማ እንደነበር የሚያሳይ ነበር፡፡
በርግጥ የሃሰት ሪፖርት ለምን ያስፈልጋል? የሚል ጥያቄ ሲነሳ በርካታ ምክንያቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ያልሰሩትን ሰርቻለሁ በማለት ለበለጠ ኃላፊነት ለመታጨት፣ በአግባቡ አልሰራህም ከሚል ግምገማ ለማምለጥ፣ መረጃን በአግባቡ ያለመያዝና በትክክል የተሰሩ ሥራዎችን ካለማወቅ፣ ከብዙ በጥቂቱ ሊሆኑ ይችላሉ፡፤
በዚህ አጋጣሚ የመረጃ አያያዝ ክፍተት አንዱ የሪፖርት መዛባት ምክንያት ነው፡፡ በእያንዳንዱ ተቋም ያለውን የመረጃ አያያዝ የሚመረምር አካል ቢኖር ለመረጃ ያለን ግንዛቤ ምን ያህል የወረደ መሆኑን መገንዘብ የሚያስችለን ይሆናል፡፡ ለምሳሌ በአገራችን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ከተጀመረ ገና አስራ አምስት ዓመታትን ብቻ ማስቆጠሩ ይታወቃል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ያለውን የዚህን ተቋም መረጃ ለማግኘት ግን አዳጋች ነው፡፡ በከተማዋ ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት ምን ያህል ቤቶች ተገነቡ? ምን ያህል ሱቆች ተገነቡ? ከነዚህ ውስጥ ምን ያህሉ ለነዋሪዎች ተላለፉ? ምን ያህሉ አሁን በተጠባባቂነት ይገኛሉ? ያልተላላለፉ ቤቶች ምን ያህል ናቸው? ምን ያህል ቤቶች ለንግድ ሱቆች በጨረታ ቀረቡ? ምን ያህሉስ ተሸጡ? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችን ብንጠይቅ መልሱ እንደናፈቀን ይቀራል፡፡ ምክንያቱም ተገቢውን መልስ ለማግኘት አዳጋች ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከዚህ ቀደም አስተዳደሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን መቁጠር መጀመሩ ማሳያ ነው፡፡
አንዳንድ ሰዎች እንደሚያነሱት እንዲህ ዓይነት መረጃዎች በግልጽ እንዳይታወቁ የሚደረገው ሆን ተብሎ ለኪራይ ሰብሳቢዎች በር ለመክፈት ነው፡፡ ምክንያቱም የጠራ መረጃ ካለ ለኪራይ ሰብሳቢው አካል በር ስለሚዘጋ ለዚህ ፍላጎት ባላቸው አካላት የጠራ መረጃ ተፈላጊነቱ አነስተኛ ይሆናል፡፡
እንግዲህ እንዲህ ዓይነት መረጃዎች የውሸት ሪፖርት አካላት ናቸው፡፡ እያንዳንዱ አካል በየዓመቱ ምን ያህል ቤቶች እንደተገነቡና ምን ያህሎቹ ለተጠቃሚው እንደተላለፉ፣ ምን ያህል ሱቆች ለጨረታ እንደቀረቡ፣ ምን ያህል እደተሸጡ ወዘተ መረጃ ለመያዝም ሆነ ለማደራጀት ከባድ ሆኖ አይደለም፡፡ ነገር ግን ችግሩ የሪፖርት ጥራት መጓደል ጉዳይ ነው፡፡
በተለይ ከታች ወደ ላይ የሚሄዱ መረጃዎች የግንዛቤ ክፍተት ያለባቸው እንደሆኑም በተለያዩ ወቅቶች ከምሰማቸው ሪፖርቶች ማረጋገጥ ችያለሁ፡፡ በተለይ በቀጥታ ከኅብረተሰቡ ጋር ግንኙነት ያላቸውና ከታች ወደ ላይ የሚላኩ ሪፖርቶች ግነት የሚበዛባቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ በየቀበሌውና በየወረዳው በየዓመቱ አደራጅተናል ተብለው ወደ ላይ የሚላኩትን ወጣቶች ቁጥር ብንደማምር በአገራችን የሥራ አጥ ቁጥር እንደማይኖር አንዳንድ ሰዎች ሲናገሩ ይሰማል፡፡
ዓመታዊ ሪፖርት ሲቀርብ አመርቂ ውጤት አስመዝግበናል፣ ውጤቱ አበረታች ነው፣ ከመቶ ፐርሰንት በላይ አፈጻፀም አስመዝግበናል፣ ወዘተ የሚሉ የቃላት ድሪቶዎችን መስማትም ለዓመታት የቆየንበት የሪፖርት ፎርማት ሆኖ አገልግሏል፡፡ እነዚህን ቃላት ሪፖርት በሚሰማባቸው ምክርቤቶች ወይም በየስብሰባዎች መስማት የተለመደ ነው፡፡
የውሸት ሪፖርት ሀገር ገዳይ መረጃ ነው፡፡ ከእቅዱ ጀምሮ አቅምን ያላገናዘበ እቅድ ማዘጋጀትና በመጨረሻም ሳይሰራ ሲቀር እንደተሰራ አድርጎ ማቅረብ ሀገርንም ሕዝብንም ይጎዳል፡፡ ውሎ አድሮም የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ መልሶ እኛኑ እንዳይበላን እንጠንቀቅ፡፡

ወርቁ ማሩ 

Published in አጀንዳ

አገራችን ከጥልቅ ድህነት መውጣት ትችል ዘንድ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ በሁሉም ዘርፍ ከፌዴራል እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን በጀት የተያዘላቸው በርካታ የልማት ሥራዎች እንዲሁም መደበኛ የመንግሥት ተግባራት ይከናወናሉ፡፡ መቼም ቢሆን ሥራ ካለ እቅድ መዘጋጀቱ አይቀርም፡፡ በተዘጋጀውም እቅድ መሠረት ሥራዎች መከናወናቸው በየወቅቱ ይለካሉ፤ ይመዘናሉ፤ ውጤታቸውም በየደረጃውም ለሚገኙ ባለድርሻ አካላት በሪፖርት ይቀርባል፡፡ ለመገናኛ ብዙኃንም የእቅድ አፈጻጸምን አስመልክቶ መግለጫ ይሰጣል፡፡
ከእቅድ እና አፈጻጸም ጋር ተያይዞ የተጠቀስውን ጉዳይ ማከናወን በተቋማትና በአመራሮቹ ላይ የተጣለ ግዴታ ነው፡፡ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያደርጉትም መታተር በመልካምነቱ ይነሳል፡፡ ግና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ያልተሰራውን እንደተሰራ እንዲሁም በተሰራው ኢምንት ተግባር ላይ ሲጠራ የሚከብድ ቁጥር ቆልለው የሚያቀርቡ ተቋማት የመበርከት አዝማሚያ ማሳየታቸው የሀሰት ሪፖርት ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ያመለክታል፡፡
በቅርቡ የትግራይ ክልል ምክር ቤት የስድስት ወር አፈጻጸሙን በገመገመበት መድረክ የሀሰት ሪፖርት በተጨባጭ የሚታይ ችግር መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ባለፈው ዓመት በክልሉ አምስት ሺ ተማሪዎች ማቋረጣቸውን የሚገልጽ ሪፖርት ቢቀርብም፤ በመስከረም ወር በተካሄደው የመስክ ምልከታ 88 ሺ ተማሪዎች ትምህርት ማቋረጣቸው ታውቋል።
የሀሰት ሪፖርት ከፌዴራል እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን በሁሉም ዘርፎች በሁሉም ክልሎች በተዋረድ የሚታይ መቋጫ ሊበጅለት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ድርጊቱ በዛም አነሰም በብዙዎቹ አመራሮች ይፈጸማል፡፡ መቋጫ ይበጅለት ሲባልም በአገሪቱ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊ ተጽእኖ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ በሚደረገው ጥረት በኢኮኖሚ መስክ የለውጥ ሥራዎች ሀሰተኛ ሪፖርት የከፋ በትሩን ያሳርፋል፡፡ ያልተሰሩ ሥራዎች እንደተሰሩ አነስተኛ አፈጻጸም ያላቸውም ተጋነው የሚቀርቡ ከሆነ በቀጣይ በጀት አመዳደብ ላይ አሉታዊ ሚና ያበረክታል፡፡ ባልተጨበጠ የቁጥር ጋጋታና የመቶኛ ስሌት ያደገ፣ መሬት ላይ ግን ያልወረደ እድገት የኢኮኖሚውን ሚዛን በትክክል ስለማይወክል አደገኛ አካሄድ ነው፡፡
የሀሰት ሪፖርት መንግሥትን ተአማኒነት በማሳጣት የሚያስከትለው ፖለቲካዊ ኪሳራም የጎላ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ የመንግሥትን አፈጻጸም የሚመዝነው በኑሮው ላይ ባመጣው የሚጨበጥ ለውጥ ነው፡፡ በየአካባቢው መሬት ላይ ያለውን እውነታም የሀሰት ሪፖርት አይሸፍነውም፡፡ «እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር» በሚል ብሂል ተቀርጾ ላደገ ማህበረሰብ አፈጻጸምን ከእነ ጉድለቱ በማቅረብ ችግሮች እንዲፈቱ፣ የለውጡ አካል እንዲሆን የሚያስተባበር እንጂ ከታች እስከ ላይ በተዘረጋ ሰንሰለታዊ የሀሰት ሪፖርት የሚደልል አመራርም ሆነ ተቋም ፖለቲካዊ ተአማኒነትን ስለሚያሳጣ በቸልታ ሊታይና በትዕግስት ሊታለፍ አይገባም፡፡
የሀሰት ሪፖርት በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ መስክ ከሚፈጥረው ሳንካ ባሻገር ማህበራዊ ቀውስ ያስከትላል፡፡ ምንም እንኳን ሌሎች ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች ቢኖሩም የሀሰት ሪፖርት ሄዶ ሄዶ ዛሬ በአገራችን ለተፈጠረው የሰላም መደፍረስም የራሱን ሚና ማበርከቱንም በሙሉ ልብ መናገር ይቻላል፡፡
በየክልሉ የሥራ ዕድል ተፈጠረላቸው ተብሎ እንደሚቀርበው ሪፖርት ቢሆን አሁን በየስፍራው በሚደረጉ ሁከቶች የሚሳተፉ ወጣቶች አይኖሩም ነበር የሚለውን ከኅብረተሰቡ የሚሰነዘር አስተያየት ለመቀበል እንድንዳዳ የሚያደርጉ በርካታ አሃዛዊ መረጃዎችን ስንሰማ መክረማችን ለዚህ አብይ ማስረጃ ነው፡፡ በሥራ የተያዙ እጆች መንገድ በመዝጋት የኅብረተሰቡን እንቅስቃሴ ለማወክ ጊዜ የላቸውም፡፡ በሥራ የተወጠሩ አእምሮዎች ለእኩይ ተግባር ባዶ ቦታ አይኖራቸውም፡፡ ስለዚህ በሀሰት ተፈጠሩ የሚባሉት ሥራ ዕድሎች ሲፈተሹ ከሪፖርት ማድመቂያነት አለማለፋቸው አሁን አገሪቱ እየተጋፈጠች ላለችው እውነታ እንድትዳረግ አንድ ምክንያት መሆኑን በማመን ፈጥኖ መፍትሄ ማበጀት ይገባል፡፡
የሀሰት ሪፖርትን ለመግታት ምክንያቱን መመርመር ተገቢ ነው፡፡ ከጊዜ ወዲህ በተለያዩ መስኮች በሚደረጉ ውድድሮች ሞዴል ፈጻሚዎችንና ተቋማትን በመለየት ተሸላሚ የማድረግ ሂደቱ በሀሰት ሪፖርት ቁንጮ ለመባል እየገፋፋ ነው በሚል እንደ አንድ ምክንያት ይቀርባል፡፡ በተሰጠው እቅድ መሠረት ባለመስራት ከሚመጣ ተጠያቂነት ለመሸሽና ሌሎች ሰበቦች ለችግሩ በምክንያትነት ይቀርባሉ፡፡
ምንም ሆነ ምን ለሀሰተኛ ሪፖርት የሚቀርብ ምክንያት ተቀባይነት ስለማይኖረው በዘላቂ መፍትሄ ላይ መምከርና ውሳኔ ማሳለፍ ተገቢም፤ ወቅታዊም ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በሀሰት ሪፖርት ቀርቦ እንደነበር በተነሳበት የትግራይ ክልል ምክር ቤት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጉዳዩ የፀረ ድህነት ትግል እንቅፋት እየሆነ በመምጣቱ ከመሠረቱ ለመፍታት በባለሙያዎች የሚመራ አሀዛዊ መረጃዎችን የሚያሰባስብ ተቋም በኤጀንሲ ደረጃ በክልሉ እንደሚቋቋም ጠቁመዋል፡፡
የሀሰት ሪፖርትን ለመግታት በትግራይ ክልል በእቅድ ደረጃ የተያዘው ሃሳብ በአገር አቀፍ ደረጃ ሊተገበር ይገባል፡፡ ከእዚህ ባሻገር በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶች አስፈጻሚ አካላትን ሲከታተሉ ሪፖርቶችን በአግባቡ መመርመር፣ ከመስክ ምልከታ ጋር ማመሳከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሀሰት ሪፖርት እውቅና የሚሹትን ተቋማትና አመራሮችም ለይቶ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ለጉዳዩ መቋጫ ማበጀት ግድ ይላል፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።