Items filtered by date: Saturday, 10 March 2018
Saturday, 10 March 2018 19:34

ሴቶች ለአገር ሠላም

 «በተደራጀ የሴቶች ተሳትፎና ንቅናቄ  የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት  እናረጋግጣለን»  በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን የካቲት 29 ቀን 2010 ዓ.ም ተከብሯል፡፡ በዚህ መነሻነትም  ሴቶች በአገር ሰላም ላይ ያላቸው ሚና  የጎላ መሆኑና በዚያኑ ልክ ሴቶች  ለሰላም ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው  ከተነሱ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ እኛም በሰላም ጉዳይ ላይ  የተለያዩ ሴቶች አነጋግረናል፡፡
በቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 12 ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አሰለፈች ታደሰ፤ የአገር ሰላም የህልውና  መሠረት በመሆኑ ማንኛውም ሰው ሊጠብቀው  እንደሚገባ  ይናገራሉ፡፡ እርሳቸው  እንደሚሉት፤ አገር ሰላም ካልሆነ  ወጥቶ መግባት፤ ሰርቶ ሀብት ማፍራት  አይቻልም፡፡ ሰብአዊ መብት ተጥሶ ዜጎች ለአካል ጉዳትና ለህልፈተ ሕይወት  ይዳረጋሉ፡፡ የሴቶች እኩልነትም ሊከበር  አይችልም፡፡ በመሆኑም ሰላም የሁሉ ነገር  መሠረት ነውና ሊጠበቅ ይገባል፡፡
ወይዘሮዋ  እንደሚሉት፤ ቀደም ባለው ጊዜ  ከባህል ጋር ተያይዞ  ሴቶች  የማጀት ሥራ ብቻ መስራት አለባቸው  የሚል አመለካከት በኅብረተሰቡ ዘንድ ነበር፡፡ አሁን  ላይ  ያ አመለካከት እየተሻሻለ ነው፡፡  ዛሬ  ሴቶች ከወንዶች እኩል ሀብት እያፈሩ ይገኛሉ፡፡ በፊት በቤት ውስጥ ተገድበው የነበሩት  ሴቶች  አደባባይ ላይ  መውጣት ችለዋል፡፡  ይህም የሴቶች እኩልነትና  ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ  እያደገ መጥቷል፡፡ አሁን ላይ እየታዩ  ያሉ  መልካም ጅምሮች  ተጠናክረው  እንዲቀጥሉ  ሰላም  ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም  የአገር ሰላምን በማስከበር በኩል የሴቶች ሚና የጎላ በመሆኑ  በየደረጃው ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡
ሴቶች  ለትዳር አጋራቸውም ይሁን  ለልጆቻ ቸው  ቅርብ ናቸው  ያሉት ወይዘሮ አሰለፈች፤ የአገር ሰላም ተጠብቆ የተጀመረው የልማት ጉዞ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል ምክርን በመለገስ  ከአጉል ድርጊቶች እንዲቆጠቡ  ማድረግ አለባቸውም ይላሉ፡፡  
የጉለሌ ክፍለ ከተማ  የወረዳ አንድ ሴቶች እና ሕፃናት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አበባዬ አበበ በበኩላቸው፤ ከአገር ሰላም እና ጸጥታ ጋር ተያይዞ ሴቶች  የጎላ ድርሻ  እንዳላቸውና በዚሁም  ረገድ ሰላምን በማስከበር ሥራ ላይ የራሳቸውን ሚና እየተወጡ እንደሚገኙ ያስረዳሉ፡፡
እንደወይዘሮ አበባዬ ገለጻ፤ ሴቶች ልጆቻቸውን በመምከር፣ ወደ አልተፈለገ ሁክትና ብጥብጥ እንዳይገቡ ምሳሌ  በመሆን ማስተማር ይችላሉ፡፡ በዚህም በኩል  የሰላም እጦት ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ  በማስተማር ጭምር  የአገሪቱን ሰላም ለማስጠበቅ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም ሴቶች የሰላም አምባሳደር መሆናቸው በመላው የአገሪቱ ክፍል  ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
አገር ሰላም ሲሆን  የተጀመረውን  የሞክራሲ ግንባታና የልማት ሥራዎች   ማስ ቀጠል ይቻላል ያሉት ወይዘሮ አበባዬ፤ ይሄን  ሴቶች ጠንቅቀው  ስለሚያውቁ ሰላም  በማስከበር  ረገድ  የማይተካ ሚናቸውን  መጫወት አለባቸው፡፡ ሰላም ከሌለ   ሴቶች ራሳቸውን ለመቻል በኢኮኖሚ የሚያደርጉት  እንቅስቃሴ ሊገደብ  የሚችል ስለሆነ  በፀጥታው ጉዳይ ላይ  ልዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት ይገባቸዋል፡፡
የልደታ ክፍለ ከተማ ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ መብራት ተስፋ በበኩላቸው፤ በአገሪቱ  አንዳንድ አካባቢዎች  የሰላም መደፍረስ ሁኔታዎች እየተስተዋሉ ናቸው፡፡ ይሄን ሂደት  በጋራ   ልንከላከለው ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙ ራእይ ያለው ሕዝብ በመሆኑ፤ ሃሳቡን እና ህልሙን ከዳር ለማድረስ በሰላም፣ በፍቅርና በአንድነት  መኖር አለበት፡፡
«ለቀጣዩ ትውልድ የበለጸገች ኢትዮጵያን ገንብተን ማስተላለፍ አለብን» ያሉት ምክትል ሰብሳቢዋ ለዚህ ስኬት ሴቶች የሰላም አምባሳደር ሆነው  መስራት  አለባቸው፡፡ሁከትና ብጥብጥ  ኢትዮጵያን አይገልጽም፡፡ ወደ ፊትም ሊያስኬዳት አይችልም፡፡ ይልቁንም  እየተገነባ ያለውን ኢኮኖሚ ወደ ኋላ የሚመልስ ነው፡፡ ይህን ደግሞ መንግሥትም ይሁን ኅብረተሰቡ ሊገነዘበው ይገባል፡፡ በመሆኑም ሴቶች  በአገሪቱ  አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን እየተወጡ አገሪቱ  የጀመረችውን   የልማት ጉዞ ወደፊት ማስቀጠል አለባቸው፡፡ ከአገሪቱ ኢኮኖሚ እኩል ተጠቃሚነታቸውን ሊያረጋግጡ ይገባል ብለዋል፡፡
የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ የሴቶች ንቅናቄ  የሥራ ሂደት አስተባባሪ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ነጋሽ  እንደሚናገሩት፤ በአገር  ውስጥ ሰላም ከሌለ የሴቶች ተጠቀሚነት መኖር አይችልም፡፡ በሰላም መናጋት ምክንያት ግንባር ቀደም ተጠቂ የሚሆኑት  እናቶች እና ሕፃናት ናቸው፡፡ በመሆኑም ሰላም ለሰው ልጅ ከሚያስፈልጉት ነገሮች አንዱና  ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ በመሆኑ፤ ሴቶች አስፈላጊነቱን በማመን ሊጠብቁት ይገባል ይላሉ፡፡
እንደ የሥራ ሂደት  አስተባባሪዋ  እምነት፤ ሰላም እናቶች ተረጋግተው እንዲሰሩ፣ ወልደው እንዲያጠቡ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ከሌሎች  የኅብረተሰብ ክፍሎች በተለየ መልኩ ሰላም ለሴቶች ዋጋ አለው፡፡ በአጠቃላይም  የአገርን ሰላምና ደንነት መጠበቅ የሴቶች  ብቻ ባይሆንም ይበልጥ ተጠቂዎቹ  እነሱ  በመሆናቸው  ለየአካባቢያቸው ሰላም መጠበቅ  ዘብ መቆም ይኖርባቸዋል፡፡
የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር   ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ  ዓለም ፀሐይ ኤልያስ  በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ   የቀድሞ አባቶች በአንድነት ድርና ማግ ሆነው ለሰላሟ  ዘብ በመቆም ለዛሬው ትውልድ ያስረከቧት አገር እንደሆነች ያብራራሉ፡፡ ለእዚህም  የአድዋ ድል  ህያው ምስክር መሆኑን ያስታውሳሉ፡፡
በአንድ አገር  ውስጥ  የሰላም ዋጋ ተመን  የለሽ እንደሆነ  የተናገሩት ኃላፊዋ፤ ሴቶች ሰላም ለአንድ አገር እድገትና ብልጽግና  ያለውን ፋይዳ ተገንዝበው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ  በአገሪቱ እየተንፀባረቁ  የመጡ  የሰላም ማጣት ችግሮችን  በመፍታት  የአገሪቱን የልማት ጉዞ  በማስቀጠል  ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው  ብለዋል፡፡
ሴቶች የአገራቸውን ሠላም ለማረጋገጥ  በአካባቢያቸውም  ሆነ  በቤታቸው  የሠላም ጉዳይ  የዕለት ተዕለት  ሥራ በማድረግ የማይተካ ሚና መጫወት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ   አስተዳደር ከንቲባ የሕዝብ ግንኙነት ዋና አማካሪ አቶ ተወልደ ገብረፃዲቅ እንደሚናገሩት፤ አገሪቱ የጀመረችውን የህዳሴ ጉዞ ለማስቀጠል  የሰፊውን ሕዝብ ሁለገብ ተሳትፎ  የሚጠይቅ ነው፡፡ በዚህም  የሴቶች  ሚና የላቀ ነው፡፡ በመሆኑም ሴቶች  አገሪቱ የጀመረችውን የልማት ጉዞ ለማስቀጠል ፋይዳው ወደር የሌለው በመሆኑ ሰላማቸውን በማስጠበቅ ተሳትፎቸውንና ተጠቃሚነታቸውን ለማስፋት በቁርጠኝነት መስራት አለባቸው ይላሉ፡፡
«የሴቶችን ተጠቃሚነት  ለማረጋገጥም ሆነ  የልማት  ሥራዎችን ለማከናወን ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ አስፈላጊ ነው» ያሉት አቶ ተወልደ፤ እንደ ቀድሞ ሁሉ የአገሪቱ ሰላምና ፀጥታ  አስተማማኝ ሆኖ እንዲቀጥል ሴቶች ግንባር ቀደም  በመሆን  ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ሴቶች የሰላም ማጣት የሚያስከትለውን ጉዳት  ከማንም በላይ ይገነዘባሉና በአገራችን  ሰላም  እንዲሰፍን ከማንም በፊት ትኩረት ሰጥተው መስራትና መታገል አለባቸው።

ሰብስቤ ኃይሉ

Published in ማህበራዊ

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን ሰባተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ አራት የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ለመጀመሪያ ጊዜ ተፋላሚ የሆኑበት ጨዋታ ባለፈው ሐሙስ ተጀምሯል። ውድድሩ የግድቡን መልካም አላማ ከመደገፍ ጎን ለጎን አራቱ ክለቦች የመጀመሪያውን ዙር የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ ለሁለተኛው ዙር የሚያደርጉትን ዝግጅት መፈተሻም ሆኖላቸዋል።
ከትናንት በስቲያ አሥራ አንድ ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ኢትዮጵያ ቡና ኤሌክትሪክን የገጠመበት ጨዋታ ተጠባቂ ነበር። ጨዋታው ከታሰበው በላይ በኢትዮጵያ ቡና ውብ ደጋፊዎች ያሸበረቀ ከመሆኑ ባሻገር የፕሪሚየር ሊግ ትልቅ ጨዋታ ወይንም የዋንጫ ይመስል ነበር። የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ከጨዋታው በላይ ለክለቡ ያላቸው ታማኝነት በየትኛውም የውድድር ዓይነት እንደማይሸረሸር በተለመደው ውብ የድጋፍ ዜማ አስመስክረዋል። ናይጀሪያዊ አጥቂ ሳሙኤል ሳኑሚና ወንድይፍራው ጌታሁንም ሁለት ግቦችን ከመረብ አሳርፈው ኤሌክትሪክን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ ማራኪውን ደጋፊ አስደስተዋል። ኮትዲቯራዊው አጥቂ ዲዲየር ሊብሬ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከሽንፈት ያላዳነችውን ግብ ከመረብ አሳርፏል።
የውድድሩ ተሳታፊ የነበሩት ደደቢትና ሲዳማ ቡና ቀደም ሲል ያደረጉት ጨዋታ ውጤትን ተከትሎም ሁለቱ ቡናዎች ኢትዮጵያ ቡናና ሲዳማ ቡና ነገ አስር ሰዓት አዲስ አበባ ስታድየም በሚደረገው የዋንጫ ፍልሚያ ሊፋጠጡ ችለዋል። ሲዳማ ቡና ሀብታሙ ገዛኸኝና ሞሀመድ አብዱልለጢፍ ባስቆጠሯቸው ግቦች የፕሪሚየር ሊጉ መሪን ደደቢትን ሁለት ለዜሮ መርታት ችለዋል። ተሸናፊዎቹ ደደቢትና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነገ ስምንት ሰዓት እዚሁ አዲስ አበባ ስታድየም የደረጃ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ውድድሩን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤትና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለአምስተኛ ጊዜ በጋራ አዘጋጅተውታል፡፡ የፍጻሜውን ጨዋታ የሚያሸንፈው ቡድን የወርቅ ሜዳልያና ዋናጫ የሚሸለም ሲሆን፣ ውድድሩን ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነው የሚያጠናቅቁት ደግሞ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚዎች ይሆናሉ፡፡

የሜይ ዴይ ጥሎ ማለፍ ውድድሮች ዛሬ ይጀመራሉ

 

የፊታችን ሚያዝያ ወር በአገራችን ለአርባ ሦስተኛ በዓለም ደግሞ ለመቶ ሃያ ዘጠነኛ ጊዜ የሚከበረውን የሠራተኞች ቀን (ሜይ ዴይን) አስመልክቶ በሠራተኛው መካከል በተለያዩ ስፖርቶች የሚካሄደው የጥሎ ማለፍ ውድድር ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል።
የሠራተኛው የበጋ ወራት ስፖርት ውድድር ለስምንት ሳምንታት ሲካሄድ የቆየ ቢሆንም ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣዮቹ ሁለት ወራት እንደሚቋረጥ የውድድሩ አዘጋጆች አሳውቀዋል። በዚህም መሠረት በበጋ ወራት ውድድሮች ተጠምደው የቆዩት የስፖርት ማህበራት ትኩረታቸውን በሜይ ዴይ የጥሎ ማለፍ ውድድሮች ላይ የሚያደርጉ ይሆናል።
በስምንት የስፖርት ዓይነቶች የሚካሄደው የጥሎ ማለፍ ውድድር ሲጠናቀቅም ከእያንዳንዱ ስፖርት አሸናፊ የሚሆነው ማህበር የፍፃሜ ጨዋታውን የሠራተኞች ቀን በሚከበርበት ወቅት ከመቀሌ ከተማ የጥሎ ማለፍ አሸናፊ ማህበር ጋር እንደሚጫወት የኢሰማኮ የስፖርት ባለሙያ አቶ ወንድሙ አለሙ ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል።
ውድድሩ ዓለምአቀፍ የሠራተኞች ቀንን አስመልክቶ የሚካሄድ እንደመሆኑ፤ ሠራተኛው የከፈለው መስዋዕትነት እየታወሰ ሠራተኛው በስፖርቱ ይበልጥ ተቀራርቦ መብትና ጥቅሙን በማስጠበቅ ያልተደራጀው ተደራጅቶ ኢንዱስትሪውን ብሎም አገሩን የሚያሳድግበት መሆኑን የኢሰማኮ ማህበራዊ ጉዳይ ኃላፊና የስፖርት ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ፍሰሐጽዮን ቢያድግልኝ ተናግረዋል። ኢንዱስትሪ በአገሪቱ እየሰፋ ሲሄድ በስፖርቱም ታግዞ ሠራተኛው ጤንነቱን የጠበቀ አምራች መሆን እንዳለበት የጠቆሙት አቶ ፍሰሐጽዮን ከዓለም አቀፍ ሠራተኛ ማህበር ጋር በመሆን ዓለምአቀፍ ተሞክሮን ቀስሞ የሠራተኛውን መብት የማስጠበቅ ጥረቱ እንደሚቀጥልም አብራርተዋል።
የጥሎ ማለፍ ውድድሮቹ ዛሬና ነገ በአዲስ አበባ በተለያዩ የማዘውተሪያ ስፍራዎች ሲጀመሩ በእግር ኳስ ስምንት ጨዋታዎች በአስራ ስድስት ማህበራት መካከል የሚከናወኑ ይሆናል። በተመሳሳይ በቮሊቦልና ጠረጴዛ ቴኒስ ውድድሮች በአራት ጨዋታዎች ስምንት ማህበራት የሚፎካከሩ ይሆናል። በከረንቦላ፣ዳማ፣ቼስ፣ዳርትና ገበጣ ጨዋታዎችም የተለያዩ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ።

ቦጋለ አበበ

Published in ስፖርት

የ2018 የካፍ ቶታል ቻምፒዮንስ ሊግና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታዎች ካለፈው ረቡዕ አንስቶ በተለያዩ የአፍሪካ ከተሞች ተከናውነዋል። አዲስ አበባና ሐዋሳ ከተማም እነዚህን ጨዋታዎች ካስተናገዱ ከተሞች መካከል ይገኙበታል። የ2009 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ አሸናፊው ቅዱስ ጊዮርጊስ በቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ የዩጋንዳውን ቻምፒዮን ኬሲሲኤንን አዲስ አበባ ላይ ሲያስተናግድ፤ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ አሸናፊው ወላይታ ዲቻ ሐዋሳ ኢንተርናሽናል ስታድየም ላይ የግብፁን ዛማሌክ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ፍልሚያ አስተናግዷል። እነዚህ ጨዋታዎችም ያልተገመቱ ውጤቶችን ከማስተናገዳቸው ባሻገር የተጠበቀው ሳይሳካለት ያልተጠበቀው ጣፋጭ ድል ያጣጣሙበት ሆነዋል።
የፈረሰኞቹ ሰዶ ማሳደድ
የአስራ አራት ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፉት አራት ተከታታይ ዓመታት የሊጉን ዋንጫ ካለተቀናቃኝ የግሉ ማድረግ ቢችልም በዘንድሮው የውድድር ዓመት እያሳየ ያለው ደካማ አቋም ደጋፊዎቹን ሊያስደስት አልቻለም። ፈረሰኞቹ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ አምና በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ስምንት ውስጥ ለመግባት ጫፍ የደረሰ ቢሆንም ዘንድሮ ያንን ታሪክ ስለመድገሙ በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች ስጋት አላቸው።
ለዚህም ባለፈው ረቡዕ በሜዳቸው የዩጋንዳውን ቻምፒዮን ኬሲሲኤን አስተናግደው ካለምንም ግብ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ያሳዩት ደካማ ሊባል የሚችል አቋም ማሳያ ነው።
ፈረሰኞቹ በሜዳቸውና በአስደናቂው ደጋፊያቸው ፊት ጨዋታውን እንደማከናወናቸው ካለምንም ግብ ይለያያሉ የሚል ግምት አልነበረም። በርካታ የስፖርት ቤተሰቦችም ፈረሰኞቹ ከአንድ በላይ ግብ አስቆጥረው የመልስ ጨዋታው ላይ የሚኖርባቸውን ጫና እንደሚቀንሱ ተማምነው ነበር። ይሁን እንጂ በሜዳቸው የነበረውን ዕድል በወጣት ተጫዋቾች ለተዋቀረው ተጋጣሚያቸው አሳልፈው በመስጠት ሰዶ የማሳደድ ዕጣ ፈንታ ገጥሟቸዋል። አምና በዚሁ የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ያጠናቀቀው አጥቂው ሳላዲን ሰዒድም ቢሆን ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኋላ ወደ ሜዳ ተመልሶ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ቢያደርግም ፈረሰኞቹን ሊታደግ አልቻለም። ይሁን እንጂ ሳላዲን እጅግ ማራኪ ድባብን ከፈጠረው ደጋፊ አድናቆት ሳይቸረው አልቀረም። ፈረሰኞቹ በዚህ ቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ላይ በፕሪሚየር ሊጉ እያሳዩት የሚገኘውን ደካማ አቋም መድገማቸው ቢያስተቻቸውም አዲሱ አሰልጣኝ አዲስና በክለቡ ባልተለመደ አጨዋወት ቡድኑን ገና እየገነቡት ከመሆኑ አንፃር ሽግግር ላይ ናቸው።
ፈረሰኞቹ የሜዳ ተጠቃሚነታቸውን አሳልፈው በመስጠታቸው ብቻ ከሳምንት በኋላ በመልሱ ጨዋታ ፈተና የሚገጥማቸው ቢሆንም የቻምፒዮንስ ሊጉ ተስፋቸው ሙሉ ለሙሉ አልተሟጠጠም። ሃምሳ ሃምሳ የሆነ ዕድል ይዘው ወደ ዩጋንዳ የሚጓዙ ከመሆኑ አንፃር በሜዳቸው ግብ ባያስቆጥሩም ካለምንም ግብ አቻ መለያየታቸው በራሱ በውድድሩ ለመቆየት ግማሽ ተስፋ እንዲኖራቸው ያደርጋል። ይህ የሚሆነው ግን በሜዳቸው ካሳዩት አቋም ተሻሽለው መቅረብ ሲችሉ ብቻ ይሆናል።
የመጀመሪያ ማጣሪያ ጨዋታቸውን ከሱዳኑ ዋኡ አል ሳላም ጋር ተደልድለው በፎርፌ ውጤት ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የተሻገሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ቡድናቸው ምንም እንኳን በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በተደጋጋሚ አቻ በመውጣት እና በመጨረሻ ባደረጉት ግጥሚያ በአዋሳ ከተማ 4 ለ 1 ተሸንፎ የለመዱት የመሪነት ሥፍራ ላይ ባይገኝም የመጀመሪያውን ዙር 15 ጨዋታዎች አከናውኖ 5 ጨዋታዎችን አሸንፎ በ8 ጨዋታዎች አቻ ሲለያይ በ2 ጨዋታዎች ሽንፈትን በማስተናገድ በ23 ነጥብ ከመሪው ደደቢት በ6 ነጥብ እርቆ በአራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ እ.አ.አ. በ1997 በአዲስ መልክ ከተጀመረ በኋላ አምና ለ21ኛ ጊዜ ሲካሄድ ሆነ በተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ያለማስተናገድ ክብረወሰኑም በግብፁ ኃያል ክለብ ዛማሌክ የተያዘ ነበር። በ2014ቱ ውድድር ዛማሌክ በቅድመ ማጣሪያው የኒጀሩ ኤኤስ ዱዋኔስ ኒያሜይን 2-0 እና 1-0፣ በመጀመሪያው ዙር የአንጎላው ካቡስኮርፕን 0-0 እና 1-0፣ እንዲሁም በሁለተኛው ዙር የዛምቢያውን ንካና 0-0 እና 5-0 በማሸነፍ በድምር ውጤት የምድብ ውድድሩን በተቀላቀለበት የ6 ጨዋታ የማጣሪያ ጉዞ ግብ ሳይቆጠርበት በመዝለቅ ያስመዘገበው ክብረወሰን አምና በቅዱስ ጊዮርጊስ መሻሻሉ ይታወሳል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2017ቱ የቶታል ቻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ የሲሼልሱን ኮት ድ ኦር በድምር ውጤት 5-0 (0-2 እና 3-0)፣ በመጀመሪያው ዙር ማጣሪያ የኮንጎ ብራዛቪሉን ኤሲ ሊዮፓርድስ በአጠቃላይ 3-0 (0-1 እና 2-0) ሲያሸንፍ በምድብ ውድድሩ የመጀመሪያ 3 ጨዋታዎች ከማሜሎዲ ሰንዳውንስ እና ኤስፔራንስ ደ ቱኒስ ጋር 0-0 ተለያይቶ የኮንጎውን ኤ ኤስ ቪታ ደግሞ 1-0 አሸንፏል። በእነዚህ 7 ጨዋታዎች ላይ መረባቸውን ያላስደፈሩት ፈረሰኞቹ ዘንድሮም የፎርፌውን ውጤት ጨምሮ ምንም ግብ አለማስተናገዳቸው በመልካም ጎኑ የሚነሳ ቢሆንም የግብ ዕድል በመፍጠርና ግብ በማስቆጠር ረገድ መሠረታዊ ለውጦችን ማምጣት እንደሚኖርባቸው ይታመናል።
የወላይታ ዲቻ ታሪካዊ ድል
በመጀመሪያው የማጣሪያ ጨዋታ የዛንዚባሩን ዚማሞቶን በድምር ውጤት 2 ለ 1 በመርታት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በቶታል ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ የተቀላቀለው ወላይታ ዲቻ በሀገር ውስጥ ሊግ አመርቂ የሚባል እንቅስቃሴ ማድረግ ባይችልም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ምንም የማሸነፍ ታሪክ ከሌለው ከግብፁ ኃያል ክለብ ዛማሌክን በሐዋሳ ኢንተርናሽናል ስታድየም አስተናግዶ ጣፋጭ ድል አጣጥሟል። ወላይታ ዲቻ በአፍሪካ መድረክ በርካታ ልምድ ያለው ከተመሠረተ 107 ዓመት የሆነው ዕድሜ ጠገቡ ክለብ ዛማሌክን ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት ማሸነፉ በብዙዎች ዘንድ ግርምትን ፈጥሯል። በሐዋሳ ኢንተርናሽናል ስቴዲየም የተገኙ ከአርባ አምስት ሺ በላይ የክለቡ ደጋፊዎችም በድሉ ጮቤ ረግጠዋል። አምስት ጊዜ የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ መሆን የቻለው ዛማሌክ አስራ ስምንት ክለቦች በሚሳተፍበት የግብፅ ሊግ በ51 ነጥብ ከመሪው አል አህሊ በ21 ነጥብ ርቆ ሦስተኛ ደረጃ ላይ እንደመገኘቱ በወላይታ ዲቻ ይሸነፋል ብሎ ያሰበ አልነበረም። በአሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሐ የሚመራው ወላይታ ዲቻ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታ ከዚማሞቶ ጣፋጭ ድል በኋላ ጅማ አባ ጅፋርን ገጥሞ ሽንፈት ካስተናገደ በኋላ ዛማሌክን ማሸነፉ በስፖርቱ ቤተሰቦች በርካታ ትርጉም እየተሰጠው ይገኛል።
ወላይታ ዲቻ ከተመሰረተ ገና ስምንት ዓመት የሞላው ክለብ ሲሆን በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እንኳን መሳተፍ የጀመረው ካለፉት አራት ዓመታት አንስቶ ነው። በአፍሪካ መድረክ ገናና ስም ያለውን ዛማሌክ መርታቱ በፕሪሚየር ሊጉ በቀጣይ ሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ወጣ ገባ አቋሙን እንዲያስተካክል ተነሳሽነትን እንደሚፈ ጥርለት ይታመናል። በሌላ በኩል ከክለቡ አልፎ ሌሎች የኢትዮጵያ ክለቦች የሰሜን አፍሪካ ኃያል ክለቦች መሸነፍ እንደሚችሉ ትምህርት የሰጣቸው ክስተትም ነው። ወላይታ ዲቻ በአፍሪካ መድረክ በቀጣይ ብዙ ርቀት ለመጓዝ ይህ ድሉ ትልቅ የመንፈስ ስንቅ ሊሆንለት እንደሚችልም ይታመናል። በዚህ የአሸናፊነት መንፈስ ወደ ግብፅ ተጉዞ ሌላ ታሪክ ይሰራም ይሆናል። ይሁን እንጂ ከድሉ ጎን ለጎን በሜዳው ግብ ማስተናገዱ ከሜዳው ውጪ ጫና እንዲበዛበት ሊያደርገው ይችላል። ይህ ጨዋታ ሁለት ለአንድ ከሚጠናቀቅ ይልቅ አንድ ለዜሮ ተጠናቆ ቢሆን ወላይታ ዲቻ ወደ ግብፅ የሚጓዘው አሁን ካለው ዕድል የተለየ ይሆን ነበር። ያም ሆኖ ግን በመልሱ ጨዋታ በየትኛውም ውጤት አቻ መለያየት ብቻ ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያሳልፈው ይሆናል።

 

ቦጋለ አበበ

Published in ስፖርት
Saturday, 10 March 2018 17:51

እንዲህም ይቀጧል

የአንድ ከተማ ከንቲባ መታሰር ትልቅ ዜና በሚሆንባት ዓለማችን፤ ከወደ ቦሊቪያ የተሰማው ዜና የግለሰብን ሳይሆን የሕዝብን የሥልጣን ባለቤትነት ያሳያል ቢባል የተጋነነ አይሆንም።
በበርካታ ሀገራት ፖለቲከኞችንና የመንግሥት ሹመኞችን ተገቢውን አገልግሎት አልሰጣችሁም ብሎ መቅጣት የሚቻለው ለምርጫ ሲወዳደሩ ድምጽ በመንፈግ ነበር። በቦሊቪያ ግን ማህበራዊ ፍትህ የሚሉት የራሳቸው የቅጣት መንገድ አላቸው ሲል በድረ ገጹ ያስነበበን ኦዲቲ ሴንትራል ነው።
ድረ ገጹ እንደሚያትተው፤ በሰሜን ቦሊቪያ የትንሿ ሳን ቦንቫንቱራ ከተማ ነዋሪዎች ከንቲባቸው የሆነውን ጃቪየር ዴልጋዶን ሕገመንግሥታዊ መብታቸውን በመጠቀም በማህበራዊ ፍትህ ለማስፈን ሲሉ ለመቅጣት በቅተዋል። በቅጣቱም ከንቲባውን በተዘጋጀው ተከርቸም ውስጥ ለአንድ ሰዓት አንድ እግሩን አስረው በማቆየት በአገልግሎቱ አለመርካታቸውን እንዲገነዘብ አድርገውታል።
ከንቲባው አንድ እግሩ በተዘጋጀው ወጥመድ መሳይ ተከርቸም ውስጥ ታስሮ በአስተዳደር ሥራው ባልረኩት የከተማዋ ነዋሪዎች፤ የደቡብ አሜሪካ ማህበራዊ ሚዲያዎችና የዜና አውታሮች ሲጎበኝ ቆይቷል። በአንድ ያልተባረከ ቀን ከንቲባው አገር ሰላም ብሎ በከተማዋና በማዘጋጃ ቤቱ ወጪ የተገነባውን ድልድይ እንዲመርቅ ወደተጋበዘበት ስፍራ ሲሄድ ነበር፤ በማህበረሰቡ ተይዞ በእንጨት በታሰራው ተከርቸም ውስጥ እግሩን ለማስገባት የተገደደው።
«ለምን እንደሚቀጡኝ እንዳውቅ እንኳ ዕድሉን አልሰጡኝም ነበር፡፡ ነገር ግን ነገሩ እንዳይባባስ አልተቃወምኳቸውም። በኋላ ግን ዕድሉን ሰጥተውኝ ተናግሬ በባላንጣዎች የተሳሳተ መረጃ ተመርኩዘው መሆኑን ሲያውቁ ይቅርታም ጠይቀውኛል» ሲል የተናገረ ሲሆን፤ የፖለቲካ ባላንጣዎቼ የሚላቸው ግለሰቦች ባለፉት ሁለት ዓመታት ለማህበረሰቡ የሰጠውን አገልግሎት ሲያጣጥሉበት እንደቆዩ፤ ይሄን የሚያደርጉት ደግሞ ግለሰቦቹ በውሃ ትራንስፖርት አገልግሎት የተሳተፉ በመሆናቸው እሱ በሚያራምዳቸው ፖሊሲዎች ጥቅማቸው ስለተነካባቸው መሆኑን ተናግሯል።
በሌላ በኩል የከተማዋ ተወላጅ የሆነው ዳንኤል ሳልቫዶር ለፋይድስ ራዲዮ እንደተናገረው ከንቲባው የተቀጣው የገባውን ቃል ባለመጠበቁና ለሕዝብም ጥያቄ ጆሮ ባለመስጠቱ ነው ሲል የከንቲባውን ሃሳብ አጣጥሏል።
ከንቲባው በማህበራዊ ፍትህ ሲዳኝ ባለፈው ሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ይሄ ሦስተኛው ሲሆን፤ በመጀመሪያ ለቅጣት የበቃው ወደሥልጣን በመጣ በጥቂት ወራቶች ውስጥ ነው። ለሁለተኛ ጊዜ የማህበረሰቡ አባላት ለሁለት ወራት ከቢሮው አግደውት የቆዩበት አጋጣሚ ሲሆን፤ በዚህም ወቅት ለሕይወቱ በመስጋት ወደ አጎራባች ከተማ ሄዶ የአካባቢው ባለሥልጣናት ለችግሩ መፍትሔ እስኪያበጁ ለመቆየት ተገዶ ነበር።
በበርካታ ማህበረሰቦች እንዳለው ሁሉ የቦሊቪያ ሳን ቦንቫንቱራ ነዋሪዎችም ራሳቸውን የሚያስተዳ ድሩባቸው (ሰነፍ አትሁን፣ ውሸታም አትሁን፣ ሌባም አትሁን፣ የሚሉ እሴቶች አሏቸው) እነዚህን እሴቶች ጥሶ የተገኘም በማህበራዊ ፍትህ የሚቀጣ ይሆናል። የእነሱን የሚለየው የማህበራዊ ፍትህ ሕጋቸውን በ2009 ዓ.ም በሕገመንግሥታቸው የተካተተ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ለቀላል ወንጀሎች ብቻ እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ ዘገባው አስነብቦናል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

Published in መዝናኛ
Saturday, 10 March 2018 17:51

ትርንጎ አማረኝ

እናንተ´ዬ ልጅ እያለሁ፤ አንተ መቼ ነው ልጅ የነበርከው እንዳትሉኝ እንጂ ትርንጎ የምትባል ቆንጆ አብራኝ ትማር ነበር፤ በብርሃንህ ዛሬ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት። መቼም የዛኔ በዛ ዕድሜዬ ፍቅር ይዞኝ ነበር ለማለት ባልደፍርም በጣም እወዳት ነበር። ከክፍላችን በር እስከ ትምህርት ቤቱ ዋና መግቢያ ድረስም ሁሌ አብረን እንሄድ ነበር። ከዚያ በኋላ ግን መስመራችን አንድ ቢሆንም ከጎኗ ለመሄድ አልደፍርም። ለዚህ ነው መውደድ እንጂ ፍቅር አልነበረኝም የምለው፤ የእኔ አመክንዮ ባይዋጥላችሁም በወቅቱ ግን ለእኔ ይህ በቂ ምክንያት ነበር።
ክፍል ኃላፊያችን ረብሻን ለመከላከል ብለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከማወጅ ቀላል መንገድ ለመጠቀም ወንድና ሴት እያሰባጠሩ ነበር የሚያቀምጡን። እናም እኔና ትርንጎ በሦስት በሦስት ክፍለ ጊዜ የተከፈለችውን የግማሽ ቀን ትምህርት የምናሳልፈው አብረን ነበር። 15 ደቂቃ እረፍትንም እንጨምራት።
ትርንጎ ከትምህርት ቤት ከቀረችም ጥሩ አጋጣሚ ደብተሯን ተቀብዬም እኔ እፅፍላት ነበር። ልብሷ አቀማመጧና ድርብ ጥርሷ መቼም በአይነ ህሊናዬ ታትሟል።
ታዲያላችሁ ከዓመታት በኋላ አብሮኝ ከተማረ ጓደኛዬ ጋር መንገድ ስንጓዝ ባጠገባችን ያለፈች አንዲትን ቆንጅዬ እየጠቆመ «ትርንጎን አትመስልም?» አለኝ።
ጊዜው በጣም ቢረዝምም ዛሬም ውስጤ ስላለችና ለሷ ያለኝን ነገር እንደሚያውቅ ስለምረዳ ትርንጎ የቷ? ለማለት አልደፈርኩም፤ ይልቁንም ምኗ ይመስላል ብዬ ቆጣ አልኩ፤
ነገሩ ገብቶታል ምን አነታረከኝ በሚል መንፈስ አታገኛትም? ማለቴ ተገናኝታችሁ አታውቁም? አለኝ
የት ነው የማገኛት? ስምንተኛ ክፍል አልፈን ቦሌ ትምህርት ቤት ስንገባ እሷ ደሴ ወደ ቤተሰቦቿ ሄዳለች፡፡
«ታዲያ ደሴ'ኮ ቅርብ ነው»
እዝች ያለችው ደሴ ሆቴል መሰለህ እንዴ? አልኩት፤ ትርንጎ መላክነህን በሃሳቤ እየሳልኩ።
እኔምለው አለኝ አቅጣጫ ሊያስት፤
«ግን ትርንጎ ከገመጥክ ስንት ጊዜ ሆነህ?»
አለ እንዴ ? አይቼ አላውቅም፤
ወዲያው ከዚሁ የቆየ! የድሮ! የጥንት... ብቻ ያሻችሁን በሉት ከጓደኛዬ ጋር የጀመርነው ወሬ ከቆንጅዬዋ ትርንጎ ወደ ፍራፍሬው ተሻገረ፤
በእውነትም ትርንጎ አይደለም ከበላሁ ካየሁ እጅግ ረጅም ጊዜ አልፎኛል፤
የፍራፍሬ አድናቂ ባልሆንም ወደ ጭማቂ ቤት ጎራ ስለምል እንዴት እስካሁን አይቼ አላውቅም ብዬ ራሴን ጠየኩት፤ ግን ላስታውስ አልቻልኩም። ኧረ! እንዲያውም ከጭማቂ ዝርዝር ውስጥም አጋጥሞኝ አያውቅም።
በዚያ ዘመን ትርንጎ የሰው ስም ብቻ አልነበረም የሚወደድና ከብርቱካንና ሎሚ ጋር ለውበት መግለጫ የሚዘፈንበትም የፍራፍሬ ዓይነት እንጂ።
እንዲያውም ሰው መጀመሪያ ለፍሬው ስም አውጥቶ ሲጣፍጠው ለሰው ያረገው ይመስለኛል። የአቀንቃኙን ስም ባላስታውሰውም
ብሩቱካን ትርንጎ መሳይ
በስሜት ልቤ አንቺን ሲያይ፤ ...የሚል ዘፈን እንደነበርም አስታውሳለሁ፡፡
እኛም እኮ ለቡሄ ሆያ ሄዬ ስንጨፍር በበር ቀዳዳ ያየናቸውን እናት አንጀት ለማራራት «ሎሚ ተረከዝ ትርንጎ ባት» እያልን እናሞግስ ነበር።
ከሃሳቤ ተመልሼ እውነት እኮ ገጥሞኝ አያውቅም አልኩት፤
«ወይ አዳቅለዋታል አልያም በአፕል ተተክታለች» አለኝ ሳቅ እየቀደመው፡፡
ለነገሩ ልክ ነህ ይሄ ሁላ ጭማቂ ቤት ሳይከፈት ብርቱካንና ሙዝን ተከትላ ሀገር አቅንታ ነበር አልኩት፡፡ በእግራችን እየተጓዝን ስለነበር እስኪ እንጠይቅ ተባብለን በአቅራቢያችን ያሉ ሦስት ተከታታይ አትክልት ቤቶችን ጎበኘን አለ የሚል አልተገኘም፡፡ ግማሹ የለም የሚለውን መልስ የሚሰጠን ፈገግ ብሎ «ትቀልዳላችሁ» በሚል ስሜት ነው። እንግዲህ እረፈው ትርንጎን ምድር አታመርት። ትርንጎም አምርራ ርቃለች።
ያው መቼም ትርንጎና ብርቱካን የሚል ስም ከነበላይነሽ አቦዘነች አበበች..... ጋር የመጥፋት አደጋ ከተጋረጠባቸው መካከል እንደሆኑ ስለማውቅ የኔዋንም (ለጊዜው የኔ ላርጋትና) አላገኛት ይሆናል የሚለው ስጋቴ ጨመረ። ማን ያውቃል ከዘመኑ ጋር ለመራመድ ስሟንስ ቀይራ ቢሆን? ግን በእውነት ......
ሙዝ እየተጨመቀ በሚጠጣበት ሀገር ትርንጎ ለአቅመ ጭማቂ ሳትደርስ ጠፍታ ይሆን?
የኔዋስ ትርንጎ ለኔ ለአቅመ ....... ሳትደርስ የት ደረሰች ? ትርንጎ ካላችሁ ....።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

Published in መዝናኛ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሁለት ሦስተኛ አብላጫ ድምፅ አፅድቋል፡፡ በትናንትናው ዕትማችን የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሰጡትን ማብራሪያና ከምክር ቤት አባላት የተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ በዛሬው ዕትማችን ደግሞ ከምክር ቤት አባላት የተነሱ ተጨማሪ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን ይዘን ቀርበናል፡፡ 

የምክር ቤቱ ሦስተኛ ተናጋሪ፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በቀጥታ በሀገሪቱ ሁሉም ክፍል በተመረጡ ቦታዎች ላይ ማወጅ ይችላል። ንዑስ አንቀጽ ሁለት አያስፈልግም የሚል ነገር አለ። ንዑስ አንቀጽ ሁለት የሚለው በአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስቱ በአዋጁ መሠረት የሚወሰደውን እርምጃና ቀረ የሚልበትን አካባቢ ይወስናል፡፡ ይህንንም ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል።
ይሄ የኮማንድ ፖስቱ ሥልጣንና ተግባር ነው። የሰዓት እላፊም ሆነ የተለያዩ ነገሮችን የሚያደ ርግባቸውን ቦታዎች እየለየ የሚሰራበት ሂደት ነው እንጂ የተፈጻሚነት ወሰን ሊሆን አይችልም። ስለዚህ ይህ ንዑስ አንቀጽ መውጣት አለበት፡፡ አዋጁም በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ተፈጻሚ ይሆናል በሚለው መሠረት መስተካከል ይገባዋል የሚል አለ።
የድብቅ ቅስቀሳ ማድረግ፣ የሚለው ቢታይ ጥሩ ነው፡፡ የድብቅ ቅስቀሳው ምን ዓይነት ነው የሚለው ራሱን የቻለ የመረጃና የማስረጃ ጉዳይ ያለበት ስለሆነ ይፋዊ የሚለው የድብቅ ቅስቀሳ፣ መታየት አለበት የሚል አስተያየት አለኝ። ሌላ ከአንቀጽ አራት ጋር በተመለከተ በሕገ መንግሥትና በሕገ መንግሥት ሥርዓት ላይ የሚቃጣ ወንጀል የጠነሰሰ፣ የመራ፣ ያስተባበረ የፈጸመ፣ ወይም በማናቸውም መንገድ በወንጀል ድርጊት የተሳተፈ ወይም ተሳትፏል ተብሎ የሚጠረጠር ማንኛውም ሰው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ስር ያደርጋል። ተገቢውን ማጣራት በማድረግም ወደ በመደበኛው ሕግ ተጠያቂ ያደርጋል ይላል።
እዚህ ላይ እየሰጠን ያለነው ሥልጣን ተገቢው ማጣራት የሚለው ኮማንድ ፖስቱ ሳይሆን ማጣራት ያለበት፣ እንዲያጣራ ሥልጣን የሰጠነው ለፌዴራል ዐቃቤ ሕግና ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ነው። ስለዚህ ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ለመደበኛ ሕግ ተጠያቂ እናደርጋለን የሚለውን ክስ የማቅረብም ሆነ በተመሳሳይ የማጣራቱን ሥራ ኮማንድ ፖስቱ የሚያደርገው ነው።
ስለዚህ እዚህ ላይ የተቀመጠው በቁጥጥር ስር ያደርጋል የሚለውና የማጣራትና በመደበኛ ሕግ ተጠያቂ ማድረግ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና በፖሊስ ኮሚሽን ሥልጣን በተሰጣቸው መሠረት አፋጣኝ የፍርድ ቤትና ፍትሐዊ የሆነ ውሳኔ ለመስጠትም የሚያግዝ ነው እንላለን። ብሔር ተኮር በሆኑ ወይም በሌሎች ጉዳዮች የተፈናቀሉ ሰዎች ከክልሉና ከአካባቢው ሕዝብ ጋር በመሆንና በመተባበር ወደ ቀድሞው መኖሪያ ቤታቸው ተመልሰው እንዲቋ ቋሙና ሰላማዊ ኑሯቸውን እንዲመሩ ድጋፍ ያደርጋል የሚለው በጣም ጥሩ አንቀጽ ነው።
ሁላችንም እንደምናውቀው ከግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ተፈናቅሎ ነው የሚገኘው። ስለዚህ ይህንን በማብራሪያ ውስጥ እንዳለና ወደቀድሞው መኖሪያቸው ተመልሰው ማቋቋሙ እንደተጠበቀ ሆኖ እንደዚሁም ወደመረጡበት፣ በፍላጎታቸው ላይ የተመሠረተ የሚለው ማብራሪያ ውስጥ በተቀመጠው መሠረት ፍቃደኝነታቸው መኖር አለበት።
ምክንያቱም ሕዝቡን አሳምነው፣ በፍላጎቱ ወደ ቦታው የሚመለስ ካለ ይመለሳል፣ የማይመለስ ካለም በክልሉ ይወሰናል ማለት ነው። ስለዚህ ፍላጎት የሚለውና ማብራሪያው ውስጥ ያለው ቢካተት። ሌላው አንቀጽ አራት ንዑስ አንቀጽ አስራ አምስትን በተመለከተ እዚህ የምናወጣው አዋጅ ተፈፃሚነት የሚኖረው በእኔ አስተሳሰብ የሚኒስትሮች ምክርቤት ካጸደቀበት ከየካቲት ዘጠኝ ጊዜ ጀምሮ ነው።
ስለዚህ ሕገወጥ የመሬት ወረራ፣ ሕገወጥ ግንባታ፣ ኢንቨስተሮችን ማፈናቀሉና የሚሰሩበትን ቦታ ከሕግ ውጪ የመውሰድ ድርጊቶችን ይከላከላል የሚለው፣ ከክልል መስተዳድሮች ጋር በመተባበርና በመደጋገፍ የሚለው ነገር ካልተቀመጠ በአንቀጽ ዘጠኝ ላይ የተቀመጠው የአንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝ የክልሎችን ሉአላዊነት እንዳይጣረስ በግልጽ መቀመጥ አለበት።
ስለዚህ ሕገ መንግሥታችንን አንቀጽ አስራ አንድን፣ አንቀጽ አስራ ስምንትን፣ አንቀጽ ሃያ አምስትን፣ አንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝ ንዑስ አንቀጽ ቁጥር አንድና ሁለት እስከተከበረ ድረስ ይህ አስተዳደራዊ ሥራ ስለሆነ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሊከሰቱ ስለሚችሉ ይህንን በተመለከተ ከክልል መስተዳድሮች ጋር አብሮ መስራት አለበት የሚለውን ማካተት አለብን።
ሌላው የማይፈቀዱ ተግባራት የሚለው ላይ የተቀመጠ ነገር አለ። ይህም በዚህ አዋጅ አፈጻጸም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ዘጠና ሦስት ንዑስ አንቀጽ አራት ሐ የተደነገገውን መተላለፍ የተከለከለ ነው። ይህ በግልጽ መቀመጥ አለበት። ምክንያቱም የተከለከሉ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? በሚለው ነው። ዝምብለን የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ ብቻ ከምናይ ከአዋጁ ቀጥሎ የሚቋቋመው የመርማሪ ቦርድ ሥልጣንና ተግባርን በተመለከተ በዝርዝር ሕገ መንግሥቱ ላይ ያለውን ነው ያስቀመጠው።
ስለዚህ በሕገመንግሥቱ ላይ ያሉትን ነገሮች ያስቀመጠ እስከሆነ ድረስ ይሄኛውም በአንቀጽ ብቻ መቀመጥ ሳይሆን አንቀጽ አንድ እንደሚለው፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ የሚለው ስያሜ አንቀጽ አስራ ስምንት ኢ ሰብአዊ ድርጊትና አያያዝ በፍጹም የተከለከለ መሆኑን ነው። አንቀጽ ሃያ ምስት የእኩልነት መብት መስፈን እንዳለበት፣ አንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝ የብሔር ብሔረሰቦች መብት፣ ቋንቋን ባህልን ነው። የሕገመንግሥቱ ምሰሶ የሆኑት ጉዳዮች መዘርዘር አለባቸው።
ምክንያቱም ከዚህ ቀጥሎ አስፈጻሚው አካል አንቀጽ ሰላሳ አራት ሀ የተከበረው ምክርቤት አውቆ እነዚህን አንቀፆች ልክ የመርማሪ ቦርዱን ሥልጣንና ተግባርን ከሕገመንግሥቱ ላይ እንደወሰድነው እነዚህም በግልጽ መቀመጥ አለባቸው። በተለይ እነዚህ አንቀጾች ሕገ መንግሥት ራሱ ያልተደራ ደራቸው ጉዳዮች ናቸው። ምንም ቢሆንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አደጋ ውስጥ ቢገባ እነዚህ መብቶች ለድርድር አይቀርቡም። በቃ በአራት ነጥብ ነው ያስቀመጠው እነዚህ ምሰሶዎች የሕገመንግ ሥታችንና የሀገራችን ህልውና ወሳኝ ስለሆኑ እነዚህ መዘርዘር አለባቸው።
ሌላው አንቀጽ ስድስት ላይ የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስቱ የመቋቋም ኃላፊነት እንደተባለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይመሩታል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የመከላከያ ሚኒስትራችን፣ የጦር ኃይሎች ኢታማዞር ሹም፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አሉ፤ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጄኔራል አሉ። እነዚህ አካላት በፌዴራል ደረጃ ነው ያሉት። የክልል ርዕሰ መስተዳድሮችን እዚህ ውስጥ ባይኖሩም የክልል ፀጥታ ኃይሎች አብረው ይሳተፋሉ፡፡ ሁሉንም ነገር መሬት ላይ ያለው አካል ይህንን ነገር ቢያደርግ ሁሉም ርዕሰ መስተዳድሮች እዚህ ውስጥ ቢሳተፉ ይህንን አዋጅ የበለጠ ሙሉ ያደርገዋል የሚል አስተያየት አለኝ።
በምርመራ የክስ ሂደትና የፍርድ ሂደት ላይ ምን ያህል መጨናነቅና የፍርድ መጓተተት እንዳለ እናውቃለን። አጠቃላይ ችሎቱን በተመለከተ ይህ ሥራ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ሥራ ነው። የኛም፣ የፍትህ አካላትም ሥራ ነው፡፡ በየደረጃው ባለው ሕገመንግሥታዊ መዋቅሩን ጠብቆ ማለት ነው። ስለዚህ በዚህ ውስጥ የክልል የፍትህ አካላት ቢሳተፉ ጥሩ ነው።
ከአገሪቱ ጠረፍ አንስቶ አዲስ አበባ ድረስ ተዘዋዋሪ ችሎት መድቦ፤ ከፌዴራል ፍትህ የተውጣጡና ከክልልም የተውጣጡ በአንድነት በቅንጅት የሚሰሩበት አካሄድ ቢፈጠር የበለጠ ጥሩ ይሆናል። የፍርድ ሂደትን እንደ ሀገር እየመራን እያስተዳደርን ያለ በመሆኑ በዚህ ዓይነት ሁኔታ መሄድ አለበት የሚል አስተያየት አለኝ።
የመጀመሪያው ሕግ እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ ሰው በአንድ ጉዳይ በሁለት ጊዜ አይቀጣም የሚለውም እንደተጠበቀ ሆኖ «እና» ብሎ አምስት ዓመት ፅኑ እሥራት ይቀጣል የሚል አለ። አንቀጽ አስራ ሰባት ላይ ደንብና መመሪያን የማውጣት ሥልጣንን በተመለከተ የተቀመጠው ጥሩ ነው። ነገር ግን የሚኒስትሮች ምክርቤት አዋጁን ለማስፈጸም ደንብ ያወጣል ነው የሚለው። መመሪያ ከመውጣቱ በፊት ደንብ ነው መቅደም ያለበት።
የሚኒስትሮች ምክርቤት ይህን አዋጅ ለማስፈጸም ደንብ አውጥቷል ወይ? የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስቱ አዋጁንና አዋጁን መሠረት ያደረገ መመሪያ ያወጣል ወይ? እዚህ ላይ ለምን ደንብ አላወጣም የሚል ነገር አለ። አንድ ላይ የተዘጋጀ ስለሆነ የሚኒስትሮች ምክርቤት ደንብ ካወጣ ጥያቄው ይቀርባል ግን ደንብ ለምን አልቀደመም? ምክንያቱም ዝርዝር ጉዳዮች የሚሰሩት በመመሪያው ነው፡፡ ደንቡ ቢቀድምም የሚል አስተያየት አለኝ።
በመጨረሻው የምሰጠው አስተያየት አዋጁ የሚጸናበትን ጊዜ በተመለከተ ነው። ይህን አዋጅ ለስድስት ወር ነው እያወጅነው ያለው። ነገርግን ይህ የስድስት ወር ጊዜ ከሕገ መንግሥታችን አኳያ በደንብ ታይቷል ወይ? በተለይ ምርጫ ዘጠና ሰባት ላይ አዲስ አበባ መስተዳድር ሕዝብ ሳይመርጠን ምክር ቤት አንገባም ብለን በአደራ ቦርድ እንደተስተዳደረ እናውቃለን።ይህ ስድስት ወር ከሆነ የሚቀጥለው የአዲስ አበባ ምርጫ በሕገመንግሥቱ ላይ ያለው የከተሞች መስተዳድር ምርጫ እሱን እንዴት ነው ያየነው?
ይህንን የምልበት ምክንያት አለኝ። የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትራችን 1992 ዓ.ም ሻዕቢያ በወረረን ጊዜና በተመሳሳይ ህወሓት በአንጃ ለሁለት ተከፍሎ በነበረበት ወቅት ምርጫ 92ን እናከናውን ወይስ አናከናውን? በሚለው ሁኔታ ላይ የመለስ አቋምን ሁሉም ሰው ያውቀዋል። «ሕዝብ ሳይመርጠን አንገባም በምንም ዓይነት በሕዝብ የበላይነትና ሕዝባዊነታችን ሳይረጋገጥ» ኢህአዴግ ሌላም ታሪክ አለው። ደርግን ካሸነፈ በኋላ ለአንድ ወር ነው በአደራ ያስተዳደረው። ከዚያ በኋላ ነበር የሽግግር መንግሥትን ያቋቋመው። ስለዚህ እኔ የምለው ምርጫው ካለ ወደ ሦስት ወይም አራት ወር ዝቅ ብናደርገው የሚል አስተያየት አለኝ፡፡
አራተኛው የምክር ቤት አባል በሰጡት አስተያየት፤ የዚህ የረቂቅ አዋጁ ዓላማ በአጠቃላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዓላማ በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥራ መንግሥትም ሕዝብም ዕለታዊ እንቅስቃሴያቸውን ለማከናወን የማይችሉበት ሁኔታ እየተፈጠረ ስላለ ይህን በማስወገድ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነበትን ሁኔታ ለማረጋገጥ ነው፤ ሌላ ዓላማ የለውም፡፡ በምክር ቤት አባላት በሁላችንም ዘንድ በዚህ ረገድ መግባባቱ አለ፡፡ አሁን የምናነሳቸው አንዳንድ ሃሳቦች ያነሱ የምክር ቤት አባላት የሕግ ይዘቱን ይበልጥ የተዋጣለት ለማድረግና ክፍተት እንዳይኖር የተሰነዘሩ ሃሳቦች ናቸው ብዬ ነው የምገነዘባቸው፡፡
በዚህ መሠረት እኔ መጀመሪያውንም ምልክት አድርጌባቸው የነበሩ የተወሰኑ ነጥቦች አሉ፡፡ አንደኛው «ይፋዊም ሆነ የድብቅ ቅስቀሳን» የሚለው አግባብ ነው የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡ በእርግጥ ሌሎች የምክር ቤት አባላት እንዳነሱት እነዚህ ነገሮች ሁሉ የድብቅ ቅስቀሳ በሚባልበት ጊዜ በቂ ማስረጃ ላይ መመስረት አለበት የሚለው ይኖራል፡፡ ግን በዚያ መልኩ መቀመጡ ትክክል ነው የሚመስለኝ፡፡ ይልቁንስ እዚያው «በምልክት መግለፅ» የሚለው ሃሳብ ምልክት ብዙ ዓይነት ምልክት ሊኖር ይችላል፡፡ እንደገባኝ ሁከትና ብጥብጥ ለማነሳሳት የሚደረግ የሚል ሃሳብ ነው ያለው፡፡ በምልክት መግለፅ ከምንል «ወይም» ከሚለው ቀጥሎ ያለውን በዚያ ቢቀመጥ ነው ጥሩ የሚሆነው፡፡
ድግግሞሹ ያን ለይቶ ማስቀመጡ ትርጉም ይኖረዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ እዚያው ላይ ንዑስ አንቀፅ 3 ላይ «ይወሳል» የሚለው «ይወስናል» ተብሎ መስተካከል እንዳለበት ይታየኛል፡፡ የመሬት ወረራና ኢንቨስተሮችን በሚመለከት የመደበኛ እንቅስቃሴዎችና አሠራሮች ይቆማሉ ማለት አይደለም፡፡ በመደበኛ ለመስራት ያልቻልነውንና ከአቅም ውጪ እየሆነ ያለውን ሁኔታ የመከላከልና የመቆጣጠር ነገር ነው ያለው፡፡
ክፍል ሦስት ላይ ሌሎች ከተናገሩት የምስማማበት የፌዴራል መንግሥትና የክልል መስተዳድሮች ለዚህ አዋጅ አፈጻጸም አስፈላጊውን በጀት ይመድባሉ፤የሚለው የፌዴራል መንግሥትን ብቻ የተመለከተ ነው የሚያስ መስለው፡፡ ይመድባል የሚለው አስፈላጊውን በጀት በየበኩላቸው የሚያንቀሳቅ ሷቸው ኃይሎች አሉ፡፡ የየበኩላቸው ሚናዎች አሏቸው፡፡ በዚህ ደረጃ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ አስፈላጊውን በጀት የሚለውን በተጨማሪም በየበኩላቸው የሚያንቀሳቅሷቸውን የሚል ታክሎበት ቢገባ ጥሩ ነው የሚመስለኝ፡፡
በተረፈ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባያስፈልገን ጥሩ ነበር፤ በፈጻሚውም ዘንድ ለኢ.ህ.አ.ዴ.ግም በአጠቃላይ በዚህ ምክር ቤት አባላት የሆነውም በሙሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የምንናፍቅበት ምክንያት የለም፡፡ አስገዳጅ ሆኖ የመጣ ነገር ነው፡፡ ይህንን አስገዳጅ ሁኔታ በአስገዳጅነቱ ልንቀበለው ይገባል፡፡ በዚህ መሠረትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዓላማን ሊሸረሽሩ የሚችሉ ነገሮችን ማስገባት የለብንም፡፡ በዚህ ውስጥ በቀረበው መሠረት ብናጸድቀው ጥሩ ይሆናል፡፡ ምክር ቤቱ መርማሪ ቦርድ ስለሚያቋቁም፤ የመርማሪ ቦርድ እንቅስቃሴን ጠንካራ እንዲሆን በማድረግ ረገድ እስከ አሁን ያለውን ተሞክሮአችንን በሚገባ አይተን እርሱን ተግባራዊ ብናደርግ ተገቢ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡
አምስተኛው ተናጋሪ በሰጡት አስተያየት፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አሁን ካለው አገራዊ ሁኔታ አንጻር አስፈላጊ መሆኑ ምንም ጥርጣሬ የለውም፡፡ አስፈላጊም፤ ወቅታዊም ነው የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡ ወቅታዊና አስፈላጊ የሚያደርገው የተዘረዘሩት ሃሳቦች አሁን ያለንበት ሁኔታ፣ በሰላም የመንቀሳቀስ፣ አርሶ አደራችን ያመረተውን ምርት በአግባቡ በትራንስፖርት ተጠቅሞ በፈለገው ቦታ የመሸጥ መብቱን፣ የመንቀሳቀስ መብቱን፣ በነፃ የመዘዋወርና ያለ ስጋት መንቀሳቀስን ያገደ ሁኔታ በመፈጠሩ ይሄ አዋጅ የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ አገር ማለት ሕዝብ ነው፡፡ ስለዚህ አዋጁ የግድ አስፈላጊ ነው የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ፡፡ ሁላችንም አንድ ዓይነት ሃሳብ ይዘን እናጸድቀዋለን የሚል እምነት አለኝ፡፡
ንዑስ አንቀጽ ሦስት ላይ ትርጓሜ ላይ በተነሳው እንደ አግባብነቱ የሚለው ባለበት ቢሄድ የበለጠ ይሆናል፡፡ እንደ አግባብነቱ በፌዴራል ወይም በክልል ወይም ደግሞ የሕግ ቃል ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ እንደ አግባብነቱ መባሉ ተገቢ ነውና ይህም አግባብ ያልሆነ ነገር ይፈጸማል ማለት አይደለም የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ፡፡ አንቀጽ አራት አንድ ላይ ይፋዊ የሆነውን የድብቅ ቅስቀሳ የሚለውን ግልጽ ማድረግ አለብን ብዬ አምናለሁ፡፡ ይፋዊ የሆነ የድብቅ ቅስቀሳ ነው የሚለው፡፡ የሚመስለው ይፋዊ የሆነ ተብሎ የተነበበ ስለነበር ነው፡፡ ግን ይህ ይፋዊም የሆነ የድብቅ ቅስቀሳ በማድረግ ብናስቀምጥ የበለጠ ይገልጸዋል የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡ ይፋዊ ሆነ የድብቅ ነው የሚለው፡፡ ግን በአነባበብ ላይ የተፈጠረ ችግር ካለ በዚያው ብናየው የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ፡፡
ከዚህ ውጪ ስለ ኢንቨስትመንት ነው ሃሳብ መስጠት የፈለግኩት፤ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራን፣ ሕገ ወጥ ግንባታን፣ ኢንቨስተሮችን ማፈናቀልን የሚሰሩበትን ቦታ ከሕግ ውጪ የመውሰድ ድርጊቶችን ይከላከላል ይላል፡፡ ከሕግ ውጪ ነው የሚለው፡፡ እኛም እንደ ምክር ቤት አባል ሕጋዊ ሥራ ይሰራ እያልን ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚለው ከሕግ ውጪ የመውሰድ ድርጊትን መከላከል አለበት ነው የሚለው፡፡ ይህን መደገፍ አለብን ብዬ አምናለሁ፡፡ በሕጋዊ መንገድ የሚሄደውንማ ይህ አላስቀመጠም፡፡ ከሕግ ውጪ ግን በኢንቨስትመንት የመጣን ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ይህች አገር የተሻለ መዋዕለ ነዋይ ለመፍጠር የውጭም ይሁን የአገር ውስጥ በኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ ዜጎች በሰላም መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ በጠበቁት መንገድ መስራት አለባቸው፡፡ እየሰሩ እያለ በሕገ ወጥ መንገድ በተለያየ አካል የምንወስድባቸው ከሆነ አገሪቷ ሙዓለ ነዋይ የመሳብ አቅሟም የኢኮኖሚ አቅሟም ይዳከማል የሚል ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ከሕግ ውጪ የሚለው መደገፍ አለበት፡፡ ይሄ ይቅር ይውጣ ማለት ያለብን አይመስለኝም፡፡ ሕግን ነው መደገፍ ያለብን የሚል ሃሳብ ስላለኝ ነው፡፡
አዋጁ እያንዳንዱን ነገር ሊይዝ አይገባም የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡ ደንብ አለው፡፡ አዋጁ በደንቡ ይብራራል፤ ከደንብ ቀጥሎ በመመሪያ ይብራራል ብዬ አምናለሁ፡፡ ሌላ ደንብና መመሪያ የማያስፈልግ ከሆነ አዋጁ ወደ መመሪያነት ነው የሚወርደው፡፡ ዝርዝር ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ይህንን አይተን አዋጁን ብናጸድቀው የአገራችንን ዜጎች ሰላም፣ የዜጎችን በነፃነት የመንቀሳቀስና በመንግሥታችን ላይ እምነት የማሳደሩን በተለይም አንቀጽ 32 ሕገ መንግሥታችን በነፃነት የመዘዋወርና ሀብት የማፍራት መብትን የሚያስከብር ነውና ማጽደቅ አለብን የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ ፡፡
ይቀጥላል

በጋዜጣው ሪፖርተሮች

 

 

 

Published in ፖለቲካ

ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ከሚካሄዱ 10 ታላላቅ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ውስጥ በዋጋ 54 በመቶውን እንደምትይዝ የ2017 ዲሊዮት የተባለ አንድ ሪፖርት አመላከተ። የአፍሪካ ኮንስትራክሽን ሪፖርት እንደሚጠቁመው ደግሞ፤ ከዚህ ውስጥ በመገንባት ላይ ያሉት የኃይል ማመንጫ ግድቦችና የባቡር መስመሮች ሰፊውን ድርሻ ይይዛሉ ይላል። ባለፈው ዓመት የነበረው የመሠረተ ልማት ግንባታ ቁጥር 65 በመቶ ያህል መጨመሩንም ነው ያስታወቀው። ይህ በአገሪቱ የመሠረተ ልማት ሥራ መጠናከሩን በሚገባ ለመረዳት ያስችላል።
በአገሪቱ ያለው የመሠረተ ልማት ግንባታ የሕዝቦችን ችግር እየፈታ መሆኑን፤ የንግድ ትስስሩ እንዲፋጠንና የኢኮኖሚ አቅሟ እንዲያድግ እያደረገ መሆኑንም ያሳያል። በተለይም በትራንስፖርት ዘርፉ ከፍተኛ ለውጥ ማስመዝገቧን ያመላክታል። ለዚህም ያሉት ለውጦች በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሃሳባቸውን ያጋራሉ።
ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ አቪዬሽኑ ቀልጣፋና ኢኮኖሚያዊ የአየር አገልግሎት በመስጠቱ ማህበረሰቡ በፈለገው ጊዜ የፈለገውን ጉዳይ እንዲፈጽም እያደረገ ነው። በተለይም የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የአየር ማመላለሻ መስመሮችን በመዘርጋት አስተማማኝ አገልግሎት መስጠት ችሏል። ይህም በአገራት መካከል ያለ የኢኮኖሚ ትስስር እንዲጠናከር ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠረና የእርስ በርስ ልምድ ልውውጦች እንዲሰፉ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ሥራ ተከናውኗል። በኢትዮጵያ አየር ክልል ውስጥና በውጭ አገራት ያሉ አጠቃላይ መረጃዎችን በመስጠትም አገሪቱ የተሻለ አቅም ላይ እንዳለች በማስተዋወቅ፤ የአገሪቱ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ በአስተማማኝ ደህንነት እንዲጓዝም እያደረገ ይገኛል። ሌሎችም አገሪቱ ውስጥ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ መንገድ ከፍቷል። ይህ የሕዝቡን ችግር ከመፍታት አኳያ የማይተካ ሚና አለው። ለሥራ ዕድል ፈጠራም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል። በ2009ዓ.ም በፕሮጀክቶች የተፈጠረው የሥራ ዕድል ብዙ መሆኑን አመላክቷል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው ባለሥልጣኑ አጠቃላይ የአቪዬሽኑ ተሳትፎ እንዲያድግ ብሔራዊ አየር መንገዱን ጨምሮ ለ12 የአየር በረራ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ፈቃድ መስጠቱን ይናገራሉ። በመላው አገሪቱ አራት ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ማረጋገጫ እንዲያገኙ አድርጓል። በተመሳሳይ 152 አውሮፕላኖች በመመዝገብ፣ በክልሎች ላይ የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማማዎችን በመገንባት የትራንስፖርት አማራጮች እንዲሰፉ አስችሏል።
የአየር ትራንስፖርት ዘርፉ ዘመኑ የሚፈልገውን ቴክኖሎጂ እንዲጠቀም በማድረግ የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣት ላይ ይገኛል። በሥራ ዕድል ፈጠራ ብቻ ብዙዎችን ተጠቃሚ አድርጓል። የእርስ በእርስ ትስስርን ለማጠናከርም መዳረሻዎችን የማስፋት ሥራ እያከናወነ በመሆኑ የተሻለ ለውጥ መታየቱን ያስረዳሉ።
እንደኃላፊው ማብራሪያ፤ የአየር ትራንስፖርት ግንባታው መስፋት ሕዝቡን በገንዘብ ቁጠባ ብቻ ሳይሆን፤ በሰዓትም ተጠቃሚ እንዲሆን አድርጓል። የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውም በዚያው ልክ ፈጣንና ቀልጣፋ እንዲሆን ያስችላል። በተለይም የሚበላሹ ምግቦችና ሌሎች ሸቀጦች ለተጠቃሚም ሆነ ለነጋዴው በጊዜው እንዲደርስ ያግዛል። ስለዚህም በቀጣይም ይሄና መሰል አሠራሮቹ እያደጉ እንዲሄዱና ሰፊ አማራጭ እየሰጡ እንዲጓዙ ለማድረግ ይሰራል።
በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተፈራ በበኩላቸው፤ በትራንስፖርት ዘርፍ አገሪቱ በጥሩ ሁኔታ ላይ ትገኛለች። በባቡር ዘርፉ ደግሞ ጥሩ መሻሻሎች እየተፈጠሩ ናቸው። ከቀላል ባቡር ጀምሮ እስከ ትልቁ ፕሮጀክት ድረስ አገሪቱ እየገነባች በመሆኑ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። በቀጣይም ቢሆን ብዙ ፕሮጀክቶች ስላሉ የሥራ ዕድል ፈጠራው የሚቋረጥ እንደማይሆን ይናገራሉ።
ባቡር በባህሪው ረጅም መንገዶችን ያቆራርጣል፤ ስለዚህም በርካታ መንገደኞችንና ጭነቶችን ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው ያዘዋውራል። ይህ ደግሞ የንግድ ሥራው የተሳለጠ እንዲሆን፣ በየመስመሩ ላይ ያሉ የግብርና ውጤቶችም ሆኑ የኢንዱስትሪ ምርቶች ገበያ እንዲያገኙ ሰፊ ዕድል ያመቻቻል። የልማት ሥራው ፈጣንና ቀልጣፋና በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ተጠቃሚነቱ እየሰፋ ነው፡፡ የልማት አስተሳሰቡም በዚያው ልክ እየጎለበተ ይገኛል። በተለይ መንግሥት ይህንን በማከናወኑ በማህበረሰቡና በመንግሥት መካከል ያለው መስተጋብር እየተጠናከረ መሆኑን ያስረዳሉ።
በተለያዩ የባቡር ዝርጋታዎች እስከ አሁን26ሺ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ከመካከለኛ የጉልበት ሥራ እስከ ቀላል ቴክኒካዊ ሥራዎች በመሰማራት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ይናገራሉ። በቀጣይም ሁኔታውን ለመቀየር የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ ሲሆን፣ የራሱን የማሰልጠኛ ተቋም ለማቋቋም የዲዛይን ሥራው መጠናቀቁን ያስረዳሉ። በቅርብ ጊዜ ውስጥም ግንባታው የሚጀመር ይሆናል ይላሉ። በእርግጥ በሌሎች ተቋማት የሚማሩትም ቴክኒካዊ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ የተለያዩ ሥልጠናዎች የሚያገኙበት አጋጣሚ ተመቻችቷል። ግንባታው እስኪጠናቀቅ ጊዜያዊ ሥልጠና እየተሰጠ ሲሆን፤ በዚህም ብዙዎች ተጠቃሚ እየሆኑ ነው ብለዋል። ሥራዎቹ በአገር ልጆች ብቻ እንዲከናወኑ ለማስቻል አስፈላጊው ጥረት እየተደረገ ነው።
እስከ አሁን ድረስ አብዛኛው የመሠረተ ልማት ሥራ የሚሰራው ከባንክ በተገኘ ብድር ሲሆን፤ በቀጣይ በአገር ውስጥ አቅም የመስራት ሁኔታን ማስፋት ያስፈልጋል። በመሆኑም በራስ አቅም ለመስራት የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ለማሳተፍ ማዕቀፍ እየወጣ ነው። ግንባታውንም ሆነ ሌሎች ወጪዎችን ለመደገፍ በእስከ አሁኑ ሥራ በየጣቢያዎቹ ላይ ሞሎችን (የገበያ ማዕከል) በመገንባት አማራጭ ገቢ ማስገኛ ሥራዎች እየተሰራ ነው። ይሄ ደግሞ ግንባታውን ከመደገፉም በላይ የሥራ ዕድል ለማመቻቸት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። በዚህ ሥራ ብዙዎች ኑሯቸውን መምራት እንደቻሉበት ይገልጻሉ።
የመንገዶች ባለሥልጣን የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙም በየጊዜው በሚደረጉት የመንገድ ዝርጋታዎች ለሰዓታት ከሚደረግ የእግር ጉዞ ጀምሮ እስከ መንገድ ዓይነት አሠራሮች ድረስ ለውጦች እየመጡ መሆኑን ያስረዳሉ። በፊት በእግር 10 ሰዓት የሚፈጀው መንገድ አሁን በመኪና ከሁለት ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ መድረስ ተችሏል። ይህም ደግሞ በመንገድ ላይ የሚያልፈው ሰዓት ተጨማሪ ገቢ ማስገኛ ሥራ ላይ እንዲውል አጋዥ ነው። የበሰሉ ምግቦችም ሆኑ ሌሎች ቁሶችን ምንም ዓይነት ብልሽት ሳይደርስባቸውና ጤና ላይ ችግር ሳይፈጥሩ ለተፈለገው አላማ እንዲውሉ ያግዛል።
የግንኙነት መረቦች ተጠናክረው የንግዱ ማህበረሰብ የእርስ በእርስ ትስስር እንዲሰፋ ከማድረጉም በላይ ማህበረሰቡ በንግድ አማራጮች ላይ በስፋት እንዲሳተፍ ይረዳል። የሚፈልገውን ነገርም በጊዜው እንዲሸምት ዕድሉ እያመቻቸለት ነው የሚሉት አቶ ሳምሶን፤ የትራንስፖርት አማራጮችን በማስፋትና በመንገዶች ላይ ምቹ ሁኔታ በመፍጠራቸው አገሪቱ የኢኮኖሚ አቅሟን እንድታሳድግ ሆናለች። በተለይም የፈጣን መስመር ዝርጋታው ብዙ ችግሮችን እየፈታ ይገኛል። ይሁን እንጂ በዚያው ልክ ችግሮች መኖራቸው ለሥራው እንቅፋት እየሆነ መምጣቱን ይጠቅሳሉ።
የመንገድ ዝርጋታ በሚደረግበት አካባቢ የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ካሳ ተሰጥቷቸውም ሆነ ሳይሰጣቸው የማይነሱበት አጋጣሚ በመስፋቱ የመንገድ ዝርጋታው እንዲጓተት እያደረገ ነው። ይህ ደግሞ ሁለት ዓይነት ኪሳራ አለው። የመጀመሪያው መንገዱ በታሰበት ጊዜ ያለመድረሱ፤ ሌላው ደግሞ ኮንትራክተሩ ሙሉ መሣሪያውንና የጉልበት ሠራተኞችን ይዞ በቦታው ላይ ስለሚገኝ ካሳ መጠየቁ ነው። ስለዚህም ተቋሙ በመጓተቱ የተነሳ ተጠያቂ እየሆነ መምጣቱን ይገልጻሉ። በተመሳሳይ የኮንትራክተሮች ሙሉ ንብረት ይዞ አለመምጣት፣ ተገቢ ያልሆነ ካሳ መጠየቅና ሥራውን በጥራት ያለማከናወንም ፈተና እንደሆነ ያስረዳሉ።
ባለሥልጣኑ ከፍተኛ ክትትልና ድጋፍ እያደረገ ቢሆንም የማህበረሰቡ ድጋፍ ያስፈልገዋል። መንገድ ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅና መንግሥትም ትኩረት ሰጥቶ መዋዕለ ነዋዩን የሚያፈስበት በመሆኑ ለብዙዎች ሰፊ የሥራ አማራጭ ይፈጥራል። ለአብነት በስድስት ወር ውስጥ ብቻ ከ50ሺ በላይ ሰዎች የሥራ ዕድል አግኝተዋል። በቀጣይም ዘርፉ እየሰፋና ብዙ ያልተዳረሱ የገጠርም ሆነ የከተማ መንገዶች በመኖራቸው ይህንን ሊያከናውን የሚገባ የሰው ኃይል ያስፈልጋል። ስለዚህም የሥራ ዕድል የሚፈጠርላቸው ሰዎች ይበራከታሉ። ይሁን እንጂ ኅብረተሰቡ ከመንግሥት ጎን መቆም ካልቻለ ግን አሁንም ብዙ ችግሮች ይከሰታሉ። በተለይም የመንገድ ዝርጋታ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ለሥራው መፋጠን የበኩላቸውን ማድረግ እንዳለባቸውም ያሳስባሉ።

ጽጌረዳ ጫንያለው

Published in ኢኮኖሚ

የኢራን የጦር መሣሪያ አቅም መፈርጠም ለበርካታ አገራት አሳሳቢ ጉዳይ ነው። በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅ ለሚገኙት የሳውዲ አረቢያ አገሮችና ለእሥራኤል ኢራን የጦር መሣሪያ አቅሟን ማሳደጓ በፍፁም የሚዋጥላቸው አይደለም። አሜሪካና የአውሮፓ አገራትም ቢሆኑ ምንጊዜም የቴህራንን የሚሳይል እንቅስቃሴ በቅርበት ሲከታተሉ ይስተዋላል።
በኢራን ከፍተኛ ኮማንደር የሆኑት ብርጋዴር ጄነራል አሚር አሊ ሃጂ ዛዲ ከሦስት ቀናት በፊት እንደተናገሩት፤ ኢራን የጦር አቅሟን ለማጎልበት የምታደርገውን እንቅስቃሴ ጠላቶቿ ገደብ በማስቀመጥ እንቅፋት ሊሆኑባት ቢጥሩም ተቀባይነት እንደሌለው አስረድተዋል።
የኢራን የዜና ወኪል ፕሬስ ቲቪ ዘገባ እንደሚያ ትተው፤ በአገሪቱ የሚደረገው ጫና ቢበረታም ኢራን በጦር መሣሪያ ረገድ የበለጠ እየጠነከረች መጥታለች። ሃጂ ዛዲ በንግግራቸው በተለይም አሜሪካንን አብዝተው የተቹ ሲሆን፣ አሜሪካ በየዕለቱ የጦር መሣሪያ አቅሟን እያሳደገች በኢራን የሚሳይል መርሃግብር ላይ ብትሯን ታነሳለች ብለዋል። ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ከኢራን ተቃራኒ ቢቆም አገሪቱ የጦር መሣሪያ አቅሟን ከማሳደግ ወደ ኋላ እንደማትልም ጄነራሉ ገልጸዋል።
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂያን ዬቪስ ሊ ድሪን ባለፈው ሰኞ ከቴህራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በአገሪቱ የባሌስቲክ ሚሳይል ዙሪያ ምክክር ማድረጋቸው ይታወሳል። ሊ ድሪን አሁንም በኢራን የሚሳይል መርሃግብር ዙሪያ መሰራት ያለባቸው በርካታ ነገሮች መኖራቸውን ከአገራቸው መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጓቸው ቃለ ምልልሶች ሲገልጹ ተደምጠዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሙሐመድ ጃቫር ዛሪፍ አሜሪካና የአውሮፓ አገራት በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ አውጥተው የመካከለኛው ምሥራቅን ሰላም እየነሱት እንደሚገኝ በትዊተር ገፃቸው ማስፈራቸውን መገናኛ ብዙኃን ሲዘግቡት ሰንብተዋል። የኢራን እንቅስቃሴ በሙሉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የተከለከለ አለመሆኑንም ሚኒስትሩ አብራርተዋል። በዚህም «የኢራንን ሕዝብ ልክ በሳዳም ሁሴን የምዕራባውያኑ ድጋፍ ታክሎበት በተሰራ ሴራ ሚሳይል እንደወረደበት አሁን ላይ እንዲደገም አንፈልግም» ሲሉም መልዕክታቸውን አስቀምጠዋል።
ብርጋዴር ጄነራል ሳላሚ ባለፈው ረቡዕ ቴህራን የጦር መሣሪያ አውደ ርዕይ ላይ እንደተናገሩት፤ ኢራን አሁን ላይ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የበለፀገ የጦር ባለቤት ከመሆኗ በተጨማሪ ባለሙያዎቿም እጅግ እየተራቀቁ መጥተዋል። «አሁን በጦር መሣሪያ ቴክኖሎጂ ረገድ ዓለም የደረሰበት ጥግ ላይ እንገኛለን፤ እጅግ የተራቀቁና ውስብስብ የጦር መሣሪያዎች በየዓይነቱ ማምረት ችለናል» ሲሉም ጄነራሉ በስፍራው ለነበሩ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ሲገልፁ ተደምጠዋል።
ቴህራን ታይምስ እንዳስነበበው የኢራን የጦር መሣሪያ ቴክኒሺያኖች ባለፉት ዓመታት የዘመኑ አገር በቀል የጦር መሣሪያዎችን በማምረት የአገሪቱን ጦር ብቁ አድርገውታል። ይህ ግን ለቀጣናው አገራት የሚያስፈራና አደገኛ ሳይሆን በምክንያታዊነት የምትጠቀመው እንደሚሆን ዘገባው ያስቀምጣል።
በኢራን ጉዳይ ላይ የሚደረግ ጣልቃ ገብነት መቼም እንደማይታሰብና ተቀባይነት እንደማይኖረው የገለፁት ሌላኛው የአገሪቱ ከፍተኛ የጦር ኃላፊ ሆሳኒ ሳላሚ ከአል አረቢያን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል። የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚያስቀምጡት የኢራን የመጨረሻው ግብ ከሳውዲ አረቢያ ጋር ጦርነት ማካሄድ እንደሆነ ያስረዳሉ። በተለይም በየመን ኢራን ጎልታ የሃውቲ አማፅያንን በማስታጠቅ ሳውዲ አረቢያን መፈታተኗ ለዚህ በምክንያትነት ይቀመጣል። ከዚህ በተጨማሪ ቴህራን የበሺር አል አሳድ መንግሥትን በኢራን የሚደገፉትን የሂስቦላ ታጣቂዎችን በማስገባት በሳውዲ አረቢያ የሚዛወሩ አማፅያን ላይ ፈተና እንዲሆኑ ማድረጓ ይታወቃል።
ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ የቀጣናው የበላይነትን በተመለከተም የአሁኑ አቋሟ ከሳውዲ አረቢያ የተሻለ መሆኑ ግልፅ ነው። ለዚህም ነው ኢራን በጦር መሣሪያ ረገድ ጡንቻዋን ስታፈረጥም ሳውዲ አረቢያና አጋሮቿ ራስ ምታት የሚሆንባቸው። በቀጣናው ሁለት ኃያላን አይኖሩምና አንዱ ልቆ መውጣቱ የግድ ስለሚሆንም ኢራን ሳውዲ አረቢያን ልቃ መገኘቷ አሜሪካንም ይሁን አውሮፓውያንን ሊያስደስት አይችልም።
ሁለቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ጎረቤታሞች ኢራንና ሳውዲ አረቢያ ጠላትነታቸው ዘመናትን የተሻገረ ከመሆኑ በተጨማሪ የቀጣናው ሰላም በእነሱ እጅ ይገኛል። ሳውዲ አረቢያ በምዕራባውያኑ ጠንካራ አጋሮች ድጋፍ ተመክታ ለዘመናት ኢራንን በመወንጀል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያገላት ብታደርግም በቀጣናው ላይ ግን የበላይነቱን አሁንም ድረስ በእጇ ልታስገባ አልቻለችም። ቀደም ባሉት ዘመናት ከኢራን ጎን መሰለፍ ከባድ የሆነባቸው አገራት ጭምር አሁን ላይ ከጎኗ መቆም መጀመራቸው የዚህ ትክክለኛ ማሳያ ተደርጎ በብዙ የፖለቲካ ተንታኞች ይነሳል።
ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ ከሰሜን ኮሪያ በተጨማሪ አሜሪካንን በዘመናዊ የጦር መሣሪያ ዙሪያ እንደ ኢራን የተፈታተናት አገር የለም። ከመካከለኛው ምሥራቅ እስከ ላቲን አሜሪካ ድረስ ቴህራን የጦር መሣሪያ አቅሟን በማጎልበትና የአሜሪካን የጦር ኃይል አቅም በመወሰን ተፅዕኖዋን ከፍ ማድረግ እንደቻለች ይታወቃል። አሜሪካ ለዚህ አፀፋ አደገኛ ሊባሉ የሚችሉ ስትራቴጂዎችን ከመከተል በዘለለ የተለያዩ ማዕቀቦችን በመጣል ኢራን ከተቀረው ዓለም እንድትገለል ትግሏን ብትቀጥልም የተሳካላት ወይንም የሚሳካላት አይመስልም።
አሁን ላይ የአሜሪካ ዓመታዊ የጦር በጀት ከኢራን ዓመታዊ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ገቢ በሁለት እጥፍ የሚበልጥ ቢሆንም ቴህራን በየትኛውም ሁኔታ እጅ ለመስጠትና ከአሜሪካ ወታደራዊ ስትራቴጂ ጋር ስታብር አትታይም። ይልቁንም ኢራን አሜሪካን ሊያስደነብር የሚችል የተለያየ ዘመናዊ ባሊስቲክ ሚሳይልና ሌሎች ግዙፍ የጦር መሣሪያዎችን ማምረት ተያይዛለች። በሰሜን ኮሪያ ዲዛይን የተደረገው «ሻሃብ» በሚል ስያሜ በተለያየ መልኩ የተሰራው ባሊስቲክ ሚሳይል ኢራን ደረቷን እንድትነፋ ከሚያደርጓት ዋነኛው ሲሆን አሜሪካንም በዚህ መሣሪያ ምክንያት እንቅልፍ እንደማትተኛ መረጃዎች ያሳያሉ። ከዚህ መሣሪያ በተጨማሪ «ሴጂል 1 እና ሴጂል 2» በሚል ኢራን ያመረተችው ሚሳይልም አሜሪካ ላይ ሌላ ፍርሃት የሚፈጥር መሣሪያ ነው። እነዚህ መሣሪያዎች ኢራን እአአ 2008 ላይ የሞከረቻቸው ሲሆኑ መካከለኛና ረጅም ርቀቶችን የመምዘግዘግ አቅም ያላቸው ናቸው።
እአአ 2009 ላይ የአሜሪካ መከላከያ ዋና ጸሐፊ ሮበርት ጌትስ ሴጂል የተባሉት የኢራን ሚሳይሎች በአማካኝ ከሁለት ሺ እስከ ሁለት ሺ አምስት መቶ ኪሎ ሜትር ሊወነጨፉ እንደሚችሉ መናገራቸው ይታወሳል። ይህንንም የኢራን ትላልቅ ወታደራዊ ባለሥልጣናት በተለይም የመከላከያ ሚኒስትሩ ብርጋዴር ጄነራል ሙስጠፋ ሙሐመድ በወቅቱ ማረጋገጣቸው ይታወቃል። እነዚህ ሚሳይሎች ይህን ያህል ርቀት ሰባት መቶ ሃምሳ ኪሎ ግራም የሚመዝን ቦምብ ተሸክመው እሥራኤልን ብሎም ምሥራቅ አውሮፓን ድባቅ የመምታት አቅም ያላቸው ናቸው። እነዚህ ባሊስቲክ ሚሳይሎች ይህ አቅም የነበራቸው ከአስር ዓመት በፊት ነው። አሁን ላይ ኢራን የጦር መሣሪያ አቅሟን ማዘመኗ ሚሳይሎቹ የኑክሌር ቦምብ የመሸከም አቅም እንዲኖራቸው ሊያደርግ የሚችል ደረጃ ላይ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህን ደግሞ አሜሪካም ሆኑ አጋሮቿ ለሰከንድም ቢሆን ሊሰሙት አይፈልጉም።

ቦጋለ አበበ

Published in ዓለም አቀፍ
Saturday, 10 March 2018 17:41

አዋጁ ለምን ታወጀ?

በሚኒስትሮች ምክር ቤት ታወጆ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዙሪያ የተለያዩ መላ ምቶች እየተሰነዘሩ ነው። አንዳንዶቹ መላ ምቶቹ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተገነዘቡ የሚመስሉ አይደሉም። ያም ሆኖ ሰሞኑን የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያትና ከኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አቶ ሲራጅ ፈጌሳ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት በኃይል ለማፍረስ የሚደረግ አካሄድ መታየቱ፣ በበርካታ አካባቢዎች ሥርዓት አልበኝነት በመንገሡ እና የሕግ የበላይነትን መሸርሸር መጀመሩን ሚኒስትሩ ገልጸዋል። እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች የልማት አውታሮች ለውድመት እየተጋለጡ መሆናቸው፣ የዜጎችን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት መገደቡ፣ የዜጎችን በሰላም ወጥቶ የመግባት መብት መጣሱ፣ ዜጎች በፍርሃትና በጭንቀት ውስጥ መውደቃቸውና ሌሎች ጉዳዮች ለአዋጁ መታወጅ ምክንያት ሆነዋል።
እንደሚታወቀው ሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 93 ላይ እንደደነገገው ሀገሪቱ ላጋጠማት ችግር ፈጣንና ወቅታዊ መፍትሔ ለመስጠት እንዲቻል በማሰብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ታውጇል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው ኮማንድ ፖስት የአዋጁን አፈፃፀም ይመራል። እርግጥ በአንድ ሀገር ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ወቅት በርካታ ጉዳዮች ከግምት ውስጥ ይገባሉ። ሁሉም መብቶች ሊገደቡ አይችሉም። ሁሉም መብቶችም አይፈቀዱም። አስፈላጊ ናቸው የሚባሉ አንዳንድ መብቶች ላይ ገደብ ሊጣል ይችላል። ሁከትና ብጥብጥ ያባብሳሉ ወይም የሀገሪቱን ሕገ-መንግሥታዊ አንድነትን አደጋ ላይ ሊጥሉ ይችላሉ በሚባሉ መብቶች ላይ ገደብ ሊጣል ይችላል።
ምንም እንኳን የአዋጁን ሙሉ ይዘት በዚህ አጭር ጽሑፍ ለማብራራት ባይቻልም፤ ሰሞኑን የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ከሰጡት የአዋጁ ሙሉ ክፍል መግለጫ በመነሳት ገደብ የተደረገባቸውን ዋና ዋና ጉዳዮችን ለአንባቢዎቼ ማንሳት ያስፈልጋል። ማንኛውም አዋጅ የሚወጣው ተፈፃሚ እንዲሆን ነው። ይህ እንዲሆን ደግሞ በአዋጁ ላይ የተገለፁት ጉዳዮችን በጥብቅ እንዲከበሩ ማድረግና ማስከበር ይገባል። ታዲያ ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ሰሞኑን በኮማንድ ፖስቱ የተገለፀውን የአዋጁን መመሪያ አንኳር ጉዳዮችን መቃኘት ይገባል። በቅድሚያ የምንመለከተው በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ውስጥ የተከለከሉ ተግባራትን ነው። ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የሚጥስ ተግባር መፈፀም፣ የሕዝቦችን መቻቻልና አንድነትን የሚጎዳ ተግባር መከወን፣ በአሸባሪነት ከተፈረጁ ድርጅቶች አመራሮች፣ አካላትና ፀረ-ሰላም ቡድኖች ጋር ማናቸውንም ግንኙነቶች ማድረግ፣ የአሸባሪ ድርጅቶችን ዓላማ ማስፈፀም፣ ጽሑፎችን መያዝና ማስተዋወቅ፣ የትራንስፖርትን እንቅስቃሴን ማወክ፣ የሕዝብን አገልግሎት ማስተዋወቅና ማቋረጥ እንዲሁም በመሠረተ ልማቶች፣ በሕዝብ፣ በመንግሥትና በግል ንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ፣ የሕግ አስከባሪዎችን ሥራ ማወክና በእነርሱም ላይ ጥቃት መፈፀም በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ውስጥ የተከለከሉ ተግባሮች ናቸው።
ክልከላው ያልተፈቀዱ ሰልፎችና የአደባባይ ስብሰባዎች እንዲሁም ከኮማንድ ፖስቱ ፈቃድ ውጪ ማናቸውንም ሰልፍና የአደባባይ ስብሰባ ማድረግ፣ በትምህርት ተቋማትና በስፖርት ማዘውተሪያዎች አድማ ማድረግ እንዲሁም ሁከቶችንና ብጥብጦችን መፍጠር እንደማይቻል ያስረዳል። ከዚህ በተጨማሪ ሁከትና ብጥብጥ የሚያነሳሳ ቅስቀሳና ግንኙነት ማድረግ፣ አድማና ሕገ ወጥ ተግባር መፈጸም ወይም እንዲፈጸም የሚያነሳሳ ይፋዊም ሆነ ድብቅ ቅስቀሳ በማናቸውም በኩል ማድረግ ጽሑፍ ማዘጋጀት፣ ማተምና ማሰራጨት፣ ትዕይንት ማሳየት፣ በምልክት መግለፅ ወይም መልዕክት በማናቸውም ሌላ መንገድ መግለፅ፣ ማንኛውንም ህትመት ወደ አገር ውስጥ ማስገባት ወይም ወደ ውጭ አገር መላክ፣ በሞባይል፣ በጽሑፍ፣ በቴሌቪዥን፣ በራድዮ፣ በማህበራዊ ሚዲያ ወይም ሌሎች የግንኙነት ዘዴዎች መለዋወጥ ክልክል ነው።
መሠረታዊ ሸቀጦችን ከቦታ ቦታ ማዘዋወርና ስርጭቱን ማወክ እንዲሁም ባህላዊ፣ ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላትን ማወክ፣ የጦር መሣሪያ ይዞ መገኘት በሁሉም የሀገራችን ከፍሎች ውስጥ የተከለከሉ ተግባራት ናቸው። ትጥቅን በሦስተኛ ሰው እጅ እንዲገባ ማድረግና የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ ለማደፍረስ ድጋፍ መስጠት እንዲሁም ከኮማንድ ፖስቱ ፍቃድ ውጪ በፀጥታ ጉዳይ መግለጫ መስጠት የተከለከለ ነው። በአዋጁና አዋጁን ለማስፈፀም የወጡ መመሪያዎችን ማደናቀፍም አይፈቀድም።
ከላይ የጠቀስኳቸውና በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ተፈፃሚ የሚሆኑት ክልከላዎች እንደተጠበቁ ሆነው፤ በተወሰኑ የሀገራችን አካባቢዎች ኮማንድ ፖስቱ በሚወስነው አካባቢዎች የተከለከሉ ተግባራትም ይፋ ሆነዋል። ከእነዚህም ውስጥ የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ፣ የሰዓት እላፊ እገዳ፣ በተለይም በኢንቨስትመንትና መሰል ተቋማት ኮማንድ ፖስቱ በሚወስነው ጊዜ ከተፈቀደ ሰዓት በስተቀር መንቀሳቀስ ክልክል መሆኑ እንዲሁም ሁከትና ብጥብጥን ብሎም አደጋን ለመከላከል የሚደረግ እንቅስቃሴን ማወክ የተከለከለ ነው።
አዋጁን በመተግበር በኩልም የዜጎች ግዴታ ተቀምጧል። በዚህ መሠረት የተከራይን መረጃ መያዝና ማሳወቅ፣ በየደረጃው የሚገኙ የሕግ አስፈፃሚ አካላት መረጃ ሲጠይቁ የመስጠትና የመተባበር ግዴታዎች ተቀምጠዋል። የሕግ አስፈጻሚ አካላት የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስቱ የተዋረዱ የዕዝ ሰንሰለቱን ተከትሎ እንደሚዋቀር፣ እርምጃዎች ሲወሰዱ የመተባበር ግዴታም እንዲሁ የአዋጁ አካል ነው።
የሚወሰዱ ርምጃዎችን አስመልክቶም ቀደም ሲል የጠቀስኳቸውን ክልከላዎች የተላለፈ ማንኛውም ሰው፤ የሕግ አስከባሪዎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ስር የማዋል፣ አዋጁ እስከሚያበቃ ድረስ ኮማንድ ፖስቱ በሚወስነው ቦታ እንዲቆይ የማድረግ፣ ተገቢውን የተሃድሶ ትምህርት በመስጠት የሚለቀቀው እንዲለቀቅ፣ ወደ ፍርድ ቤት የሚቀርበው በሕጉ መሠረት እንዲቀርብ የማድረግ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል። እንዲሁም የአካባቢውን ፖሊስ በማሳተፍ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማናቸውም ጊዜ ብርበራ የማድረግ፣ ማንኛውንም ወንጀል የተፈጸመበትን ወይም ሊፈጸምበት የሚችለውን ንብረት የመያዝ፣ ባለበት እንዲጠበቅ የማድረግ፣ የተዘረፉ ንብረቶችን በማጣራት ለባለቤቶቹ እንዲመለሱ የማድረግ እና ሌሎች አግባብነት ያላቸውን ርምጃዎችን መውሰድ እንደሚችሉ ተዘርዝሯል።
ተጠርጣሪዎች በሚመለከታቸው የሕግ አስከባሪ አካላት በመስፈርቱ መሠረት ተጠርጣሪዎች በመለየት ተጠያቂ እንዲሆኑም ያደርጋሉ። በአዋጁ ወቅት የሕግ አስፈፃሚ አካላት ብርበራ ሲያካሂዱ፤ መታወቂያ የማሳየት፣ የፍተሻውን ዓላማና የሚካሄድበትን ምክንያት የመግለፅ፣ የቤቱ ባለቤት (ነዋሪ) ፍተሻውን እንዲከታተል የመፍቀድ፣ የአካባቢው ፖሊስና ኅብረተሰብ እንዲገኙ የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸውም ተመልክቷል። የኃይል አጠቃቀምን አስመልክቶም ሕግ አስከባሪ አካላት የአዋጁን መመሪያ ለማስፈፀም ሲንቀሳቀሱ የራሳቸውን እንዲሁም የሰዎችን ሕይወትና ንብረት በመጠበቅ አስፈላጊና ተመጣጣኝ ኃይል ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ተገልጿል። እንዲሁም መመሪያውን ለማስፈፀም ሕግ አስከባሪ አካላት በትምህርት ቤቶች፣ በዩኒቨርሲቲዎችና በሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲሁም በግልና የመንግሥት ተቋማት ውስጥ አድማ የሚያደርጉ ሰዎችን ለመያዝና ለማስቆም በመግባትና በመቆየት አስፈላጊውን ርምጃ መውሰድ ይችላሉ።
እነዚህን የአዋጁን መመሪያዎች አንኳር ነጥቦች ያነሳኋቸው ያለ ምክንያት አይደለም- ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የሀገራችንን ሰላም ወደ ነበረበት ሁኔታ ለመመለስ በሚደረው ጥረት ተሳታፊ እንዲሆን ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው። በመሆኑም የታወጀበትን ምክንያት በውል በመገንዘብ ሰላማችንን ማረጋገጥ ይኖርብናል።
ከዚህ አዋጅ በዋነኛነት የሚጠቀመው ኅብረተሰቡ ነው። ሌላ ማንም አይደለም። እንደሚታወቀው በተለያዩ አካባቢዎች ኅብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ መግባት መቸገሩን በግልፅ ሲናገር ነበር። ይህን ሁኔታ መቀልበስ የሚቻለው በዚህ መንገድ የሕዝቡን ጥቅምና ሰላማዊ እንቅስቃሴን ሊያረጋግጥ በሚችል አዋጅ ነው። አዋጁ በአንዳንድ አካባቢዎች ተገድቦ የነበረውን የዜጎችን የመንቀሳቀስ መብት የሚያስጠብቅና ለእኩይ ዓላማ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ፍላጎት የሚገድብ ነው። በዚህ አዋጅ ዜጎች ከተከለከሉ የተወሰኑ ቦታዎች በስተቀር ሕጋዊነታቸውን ጠብቀው ሊንቀሳቀሱና በልማት ሥራው ላይ ተሳታፊ ሊሆኑ ይችላሉ።
በዚህ መነሻነትም ሁሉም ዜጋ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማክበር አለበት። ለጥቆም ለአዋጁ ተፈፃሚነት ትብብር ማድረግ ይጠበቅበታል። አዋጁን የማያከበርና ለተፈፃሚነቱም ከኮማንድ ፖስቱ አባላት ለሚቀርብለት የድጋፍ ጥያቄ የማይተባበር ማንኛውም ግለሰብ በአዋጁ መሠረት ተጠያቂ መሆኑ አይቀርም። ያም ሆኖ ግን ጉዳዩ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመናድ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን የጥፋት ተልዕኮ የመታደግ ብሎም ዕድገታችን ያስኮረፋቸውን አንዳንድ የውጭ ሀገራትን የእጅ አዙር ሴራ መከላከል በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ሀገራዊ ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል።
እርግጥ የትኛውም ሀገር ወዳድ ዜጋ በእነዚህ ኃይሎች ሰላሙ እንዲደፈርስ፣ ማናቸውም ሕገ-መንግሥታዊ መብቶቹ ተነጥቀው የሥርዓት አልበኞች መፈንጫ ሆኖ ሕይወቱን፣ ሀብቱንና ንብረቱን እንዲያጣ ብሎም ሀገር አልባ ሆኖ በትርምስ ውስጥ እንዲኖር አሊያም በጎረቤት ሀገር ውስጥ የጥገኝነት ሕይወትን እንዲገፋ ይፈልጋል ተብሎ አይታሰብም። ይህ እንዳይሆን ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማክበርና ለተፈፃሚነቱ መተባበር የግድ ይላል። አዋጁ የሚቆየው ለስድስድ ወር ሲሆን፤ እንደ ሁኔታው እየታየ ሊጨምር ይችላል።
ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የሚታዩትን መጥፎ ክስተቶች በስድስት ወራት ውስጥ ገትቶ በተለመደው ሰላማዊ የሕይወት መስመር ውስጥ መግባት ያስፈልጋል። ይህን ዕውን ለማድረግም አዋጁን አክብሮና በነቃ ሁኔታ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር የሕግ የበላይነት ለማስከበር ሁሉም ዜጋ የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል።

ቶሎሳ ኡርጌሳ

Published in አጀንዳ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።