Items filtered by date: Monday, 12 March 2018

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫውን እያራዘመ መጋቢት ወር ላይ ደርሷል። አሰልቺ የሆነው ምርጫ ለአራተኛ ጊዜ መራዘሙን አስመልክቶም የዓለም አቀፉ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል (ፊፋ) ሁለት ባለሙያዎችን እንደሚልክ ሶከር ኢትዮጵያ በዘገባው አስነብቧል።
አወዛጋቢውና አሰልቺው የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ በጥቅምት ወር መካሄድ ቢኖርበትም በተለያየ ምክንያት እየተራዘመ ወራትን አሳልፏል። ምርጫው ባለፈው ጥር ወር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምርጫው የሚካሄድበትን ቀን ለፊፋና ለአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ ቀድሞ እንዲያሳውቅ ቢጠየቅም ባለማሳወቁ ምክንያት በየካቲት ወር ይካሄዳል የተባለው ምርጫ በድጋሚ ሊራዘም መቻሉን ፊፋ በላከው ደብዳቤ ማሳወቁ ይታወሳል።
ዓለም አቀፉ አካልም የምርጫ ሂደቱ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ እና ያለውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ለመገምገም ሁለት ባለሙያዎችን ወደ አዲስ አበባ እንደሚልክ የታወቀ ሲሆን፤ ስምና የሥራ ድርሻቸው ግን እስካሁን ግልጽ እንዳልተደረገ ዘገባው ያሳያል።
ዛሬ አዲስ አበባ የሚገቡት እነዚህ ባለሙያዎች ለምን ያህል ቀን የማጣራት ሥራቸውን እንደሚያከናውኑም አልታወቀም። ነገር ግን በምርጫው ዙሪያ የሚመለከታቸውን አካላት እስካሁን ባለው የምርጫ ሂደት እና አሉ በሚባሉ ችግሮች ላይ ተንተርሰው ያነጋግራሉ። በሚያደርጉት ማጣራት መነሻነትም ምርጫው መቼ እንደሚደረግ እና ስለሚኖረው አጠቃላይ ነገር ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎም ይጠበቃል።

ብርሃን ፈይሳ

Published in ስፖርት

የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በየዓመቱ ከሚያካሂዳቸው የውድድር መርሐ ግብሮች መካከል አንዱ የፔፕሲ አዲስ አበባ ክለቦች ሻምፒዮና መሆኑ ይታወቃል። ይህ ውድድር ዘንድሮም ለ35ኛ ጊዜ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሳምንቱ መጨረሻ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚካሄድ ይሆናል።
በ1975ዓ.ም የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ክለቦች ሻምፒዮና በሚል የተጀመረው ውድድር፤ ከ1991ዓ.ም ጀምሮ በሞሃ የለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር ስፖንሰርነት የፔፕሲ ክለቦች ሻምፒዮና በሚል ይካሄዳል። ባለፉት ዓመታትም ከዚህ ውድድር በመነሳት አገራቸውን በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ መወከል የቻሉ አትሌቶች ተገኝተዋል።
የውድድሩ ዋነኛ ዓላማ አዳዲስ አትሌቶችን በማውጣት ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት ነው። ለአትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድን ግብዓት ከሚሆኑት አትሌቶች መካከል በርካቶቹ ከአዲስ አበባ ክለቦች ውስጥ የተገኙ በመሆኑ፤ የክለቦች ስልጠና ምን ይመስላል የሚለውን በውድድሩ መለካት እንደሚያስችልም በፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ባለሙያ አቶ አንዱአለም ያየህይራድ ይጠቁማሉ። ክለቦቹም በሚያገኙት የውድድር መድረክ በዓመት ውስጥ ያደረጉትን ዝግጅት ለመገምገምና ከሌሎች ክለቦች ጋር ያላቸውን ወቅታዊ አቋም ለማነጻጸር ይረዳቸዋል። ክለቦችም አትሌቶችን የሚመለከቱበትና የሚመለምሉበት መድረክም በመሆን ያገለግላል።
ዛሬ በሚጀምረው ውድድር ላይም በፌዴሬሽኑ ስር ያሉ ከአንደኛ ዲቪዚዮን 6 ክለቦች እንዲሁም ከሁለተኛ ዲቪዚዮን 24 በድምሩ 30ክለቦች የሚካፈሉ ይሆናል። ክለቦቻቸውን በመወከልም 706ወንድና 416 ሴት በድምሩ 1122 አትሌቶች ተሳታፊ ሲሆኑ፤ ቁጥሩም ካለፈው ዓመት ብልጫ ማሳየቱን ባለሙያው ገልጸዋል። ውድድሩ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በተቀመጠው ደረጃ መሰረት ከ100 ሜትር እስከ 10 ሺህ ሜትር ባሉት ርቀቶች እንዲሁም የሜዳ ላይ ተግባራት እንደሚከናወንም ተገልጿል።
ክለቦቹ ለዚህ ውድድር ከፍተኛ ዝግጅት አድርገው የሚሳተፉ በመሆኑ ከፍተኛ ፉክክር ይታይበታል። የአትሌቶች ቁጥር ከመብዛቱ ባሻገር አምስት አዳዲስ ክለቦች ውድድሩን መቀላቀላቸው ውድድሩን ልዩ ያደርገዋል። ዛሬ ሁለት የፍጻሜና ሌሎች የማጣሪያ ውድድሮች የሚከናወኑ ሲሆን፤ ከሌላው ጊዜ በተለየ የመክፈቻ እና መዝጊያ ፕሮግራሞችም በውድድሩ ላይ ተካቷል። በውድድሩ አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች እንደየደረጃቸው ሜዳሊያ የሚበረከትላቸው ሲሆን፤ ከሌላው ጊዜ የተሻለ ገንዘብ የሚያገኙ ይሆናል።


ብርሃን ፈይሳ

Published in ስፖርት
Monday, 12 March 2018 18:24

እንስቶች ያደመቁት ሩጫ

ስፖርት በየትኛውም ጉዳይ ውስጥ በመግባት ተጽዕኖ ማሳረፍ የሚችል ዘርፍ መሆኑ ይታወቃል። የስፖርት አውዶች በርካታ ሰዎችን በአንድ የሚያገናኙ እንደመሆኑ መልዕክትን ለማስተላለፍ በምቹነታቸው አቻ አይገኝላቸውም። ከዚህ ባሻገር ስፖርት በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው ሁነት እንደመሆኑ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ እጁን በማስገባት አጋርነቱን በማሳየት ዘመናትን ዘልቋል፤ በማሳየት ላይም ይገኛል።
የአትሌቲክስ ስፖርት መናኸሪያ በሆነችው ኢትዮጵያ፤ ስፖርት የማህበራዊ እሴቶች አጋር መሆኑን ከሚያሳይባቸው መንገዶች መካከል አንዱ የሆነውም «የሴቶች ቀንን» አስመልክቶ የሚካሄደው የሩጫ ውድድር ነው። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሚያዘጋጃቸው ዓመታዊ ውድድሮች በትልቅነቱ ሁለተኛውን ደረጃ የሚይዘው ሴቶችን ብቻ የሚያሳትፈው የ«ቅድሚያ ለሴቶች» ሩጫ ውድድር ነው። በውድድሩም ላይ የሴቶችን እኩልነት በተመለከተ መልዕክት የሚተላለፍበት ሲሆን፤ የዘንድሮ ሩጫም «ከጥቃት ነጻ ህይወት መብቴ ነው!» በሚል መሪ ቃል ታጅቦ ትናንት ተካሂዷል።
ቅድሚያ ለሴቶች የሩጫ ውድድር መካሄድ የጀመረው በ1996 ዓ.ም ሲሆን፤ ሴቶችን ብቻ እያሳተፈ ዘንድሮ ለ15ኛ ጊዜ ተካሂዷል። ይህ ውድድር ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ለማክበርና ለመዘከር፣ ህብረተሰቡ በሴቶች ላይ የሚያደርሰውን ጫና በማስቀረት በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ፣ ለእንስት አትሌቶች ስኬት ዕውቅና ለመስጠት እንዲሁም ለውጥ በማምጣት ረገድ ያላቸውን ሚና የመደገፍና መልእክቶችን የማስተላለፍ ዓላማ ያለው ነው።
ይህንን ዓላማ የተገነዘቡ አጋር አካላት ለውድድሩ ድጋፍ የሚያደርጉ ሲሆን፤ ሴቶችን የሚያነሳሱና ለሀገራቸው የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ የሚያመላክቱ መልዕክቶችንም ያስተላልፉበታል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከ17ቱ የዘላቂ ልማት ግቦች ውስጥ አንዱ፤ ለጾታ እኩልነት ትኩረት በመስጠት ጾታዊ ጥቃቶችን ማስቆም ነው። በመሆኑም ከቅድሚያ ለሴቶች ሩጫ ጋር በመቀናጀት እየሰራ ይገኛል። በየዓመቱ የሴቶች ቀንን ወይም «ማርች 8»ን በማስመልከት የሚካሄደው ይህ ውድድርም በተሳታፊ ቁጥር እያደገ፤ ትናንት12ሺ ሴቶች ተካፍለውበታል።
ባለፉት ዓመታት ከዚህ ውድድር በመነሳትም በርካቶች በኦሊምፒክና ዓለም አቀፍ ውድድሮች አገራቸውን ሊወክሉ ችለዋል። ከእነዚህ ታዋቂ አትሌቶች መካከልም አሰለፈች መርጊያ፣ ሰንበሬ ተፈሪ፣ ጃለኒ ያኒ፣ ረሂማ ከድር፣ ሱሌ ኡቱራ፣ ማሚቱ ዳስካን እንዲሁም በለንደን ኦሊምፒክ የማራቶን ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤቷን ቲኪ ገላናን መጥቀስ ይቻላል።
በትናንቱ ውድድር ላይም እናቶች፣ ወጣቶች፣ ታዳጊና ህጻናት እንዲሁም አካል ጉዳተኛ ሴቶች በሰንደቅ ዓላማ ታጅበው፣ በአገር ባህል ዲዛይን ልብሶቻቸውን አሳምረው፣ ፊታቸውንና ሌሎች አካላቸውን በአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለም አቅልመው ውድድሩን አድምቀውታል። ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው፣ ሠራተኞች ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር፣ የአንድ ቤተሰብ አባላት፣ የትንንሽ ሴት ልጆቻቸውን እጅ የያዙና ጨቅላ ህጻናትን በጋሪ የሚገፉ እናቶችም፤ በተመሳሳይ ካናቴራ ደምቀው፤ በጠዋቱ ነበር ከሩጫው ጎዳና የተሰባሰቡት።
በውድድሩ ላይም ከ200 በላይ የሚሆኑ ታዋቂ እና ጀማሪ አትሌቶችን ጨምሮ በአራት ዘርፎች ውድድሩ ተካሂዷል። በተምሳሌት ሴቶች፣ በዲፕሎማቶች እንዲሁም ከተባበሩት መንግሥታት በተውጣጡ ተሳታፊዎች መካከልም ፉክክሩ ተደርጓል። በተጨማሪም 15 ዲፕሎማቶች፣ ሁለት ኡጋንዳውያን አትሌቶች እና 11አውስትራሊያውያን ተሳታፊዎች ነበሩ። የሩጫው ተሳታፊዎችም ከአትላስ ሆቴል በመነሳት፤ በኤድናሞል አደባባይ፣ በቦሌ ድልድይ፣ ዓለም ህንጻ፣ ደሳለን ሆቴል በማድረግ የ5ኪሎ ሜትሩን ውድድር ሸፍነዋል።
ፀሐይ ገመቹ በ15ኛው የቅድሚያ ለሴቶች የ5ኪሎ ሜትር ሩጫ በግሏ በመሳተፍ አንደኛ ሆና የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀች አትሌት ናት። ለሦስት ጊዜያት ተሳትፋ በዚህኛው ውድድር አሸናፊ በመሆኗ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማትም ነው የምትገልጸው። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች ውድድሮች ላይ የተሳተፈችው አትሌቷ የሴቶች ሩጫ ከፍተኛ ደስታ እንደሚሰጣት ትጠቁማለች። ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ውድድር እንደነበር የጠቀሰችው አትሌቷ፤ ከዚህ በኋላ ለአገሯ መሮጥ እንደምትፈልግም ትናገራለች።
ውድድሩ ከተጀመረ ጀምሮ ለ15ዓመታት ተሳታፊ የሆነችው የውብነሽ ቁምላቸው፤ አካል ጉዳተኛ ብትሆንም ከ35ደቂቃ በታች በመግባት የምስክር ወረቀት አግኝታለች። በየዓመቱ ድምቀቱ እየጨመረና አጓጊ እየሆነ ያለ ውድድር መሆኑን ገልጻ መሰል መልእክት አስተላላፊና አዝናኝ የውድድር መድረኮች ተጠናክረው ቢቀጥሉ መልካም እንደሆነ ትገልጻለች። በተለይ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ መቻላቸውን ማሳየት እንዳለባቸውም ጥሪዋን አስተላልፋለች።
የቅድሚያ ለሴቶች ሩጫ አምባሳደር አትሌት መሰረት ደፋር፤ ውድድሩ ከመነሻው ጀምሮ ባሉት 15ዓመታት ከፍተኛ ዕድገት እና ለውጥ በማሳየት እንደቀጠለ ትገልጻለች። ውድድሩ መልዕክትን ከማስተላለፉ ባሻገር ትልልቅ የሚባሉ ሴት አትሌቶችን ማፍራት ችሏል፤ ከዚህ በኋላም በርካታ አትሌቶችን ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ለማብቃት ያስችላል። ከዚህ ባሻገር ሴቶች የሚገናኙበት፣ የሚወያዩበትና አብሮነታቸውን የሚያጠናክሩበት የውድድር መድረክ በመሆኑ ተጽዕኖ መፍጠር እና ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማምጣት የሚችል ውድድር መሆኑን ታብራራለች።
በዚህ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት የኡጋንዳ ታዋቂ አትሌቶች ተሳታፊ ሆነዋል፤ ከአውስትራሊያም በተመሳሳይ አትሌቶችን ማሳተፍ ተችሏል። ከዚህ በኋላም በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልልቅ ስም ያላቸውን ሴት አትሌቶችን ለመጋበዝ መታቀዱን አትሌቷ ትገልጻለች። መሰረት ጨምራም «ይህ ውድድር ከዚህ በላይ አድጎ እና ጎልብቶ ዓለም አቀፍ ውድድር እንዲሆን ምኞቴ ነው፤ በመሆኑም ሴቶች በውድድሩ ላይ ተካፈሉ» የሚል አስተያየቷን ሰጥታለች።
በዘንድሮው የUN 2018 ቅድሚያ ለሴቶች ውድድርን በግሏ የተሳተፈችው አትሌት ፀሐይ ገመቹ የገባችበት ሰዓት 16፡05፡52 ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀችው የሱር ኮንስትራክሽን አትሌቷ ደባሽ ኪላል 16፡09፡16 በሆነ ሰዓት ውድድሯን በማጠናቀቅ የብር ሜዳሊያ አጥልቃለች። ሌላኛዋ የግል ተወዳዳሪ የኔነሽ ጥላሁን ደግሞ 16፡09፡48 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ ሆና ውድድሯን አጠናቃለች። በታዋቂ ሰዎች ዘርፍ አርቲስት አምለሰት ሙጬ፣ አሰልጣኝ መሰረት ማኔ እና አርቲስት ሄዋን(ጃኖ) ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ የተዘጋጀላቸውን ሽልማትም ወስደዋል።
ለአሸናፊዎች በአጠቃላይ 70ሺ ብር የተዘጋጀ ሲሆን፤ አንደኛ የወጣችው አትሌት ከሜዳሊያ እና ዋንጫ ሽልማት ባሻገር የ15ሺ ብር ሽልማት ተበርክቶላታል። የተምሳሌት ሴቶች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ አምባሳደሮች እና ቲ-ሸርቶቻቸውን ያስዋቡ ተወዳዳሪዎችም የተለያዩ ሽልማትን አግኝተዋል። 5ኪሎ ሜትሩን በ35 ደቂቃዎች ለገቡት ተሳታፊዎችም ከሜዳሊያ በተጓዳኝ የሴቶች ውድድር በጎ ፍቃድ አምባሳደር የሆነችው አትሌት መሰረት ደፋር ፊርማ ያለበት የምስክር ወረቀት ወስደዋል። ከውድድሩ በኋላም ኢትዮጵያውያንና የውጭ ዜግነት ያላቸው አርቲስቶች የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን በማቅረብ ተሳታፊዎችን አዝናንተዋል።

ብርሃን ፈይሳ 

Published in ስፖርት

የኢፌዴሪ መንግሥት የውጭ ጉዳይና ደህንነት ፖሊሲ የሃገራችን ብሄራዊ ጥቅምን ማዕከል በአደረገ መልኩ ከሃገሮች ጋር መልካም ግንኙነት የመፍጠር መርህን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ በዚህ መርህ መሰረት ኢትዮጵያ በምታካሂደው የፀረ ድህነት ትግል እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት አጋዥ ከሚሆን ማንኛውም ሃገር ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲያው ግንኙነት ታደርጋለች፡፡በዚህም በስኬት ጎዳና ላይ እንዳለች ለወዳጅም ለጠላትም ግልፅ ነው፡፡
መንግሥት ከምዕራብ ሆነ ከምስራቅ ሃገራት፣ ከአሜሪካም ሆነ ከሩስያ፣ ከአውሮፓም ሆነ ከቻይና፣ ከዓረብ ሃገራት ሆነ ከላቲን አሜሪካ ሃገሮች ጋር የሚያደርገው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሃገሪቱን ሉዓላዊነትና ብሄራዊ ጥቅምን ለድርድር በማያቀርብ መንገድ መሆኑ ለማንም ግልፅ ነው፡፡ ይህ አቋሙ በአስቸጋሪ ወቅትና እንዲሁም ፈታኝ ሁኔታዎች በአጋጠሙት ወቅትም የማይለወጥ ነው፡፡ ለዚህ የቅርብ ግዚያት ሁለት አብነቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡ የ1997 ምርጫን ተከትሎ የተፈጠረው ሁከትና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሃገራችን ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ናቸው፡፡ በእነዚህ አስቸጋሪ ወቅቶች በጠንካራ አቋሙ ጸንቷል፡፡ በዚህም የሃገሪቱን ተሰሚነት ምን ያህል ደረጃ ላይ እንዳለ መገንዘብ ይቻላል፡፡ይህ ለወደፊቱም ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው፡፡
አገራችን በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ተሰሚነትና ተቀባይነት ሊኖራት የሚችለው በቅድሚያ ውስጣዊ ጥንካሬን መፍጠርና በሂደትም እያዳበረች መሄድ ስትችል ነው። ውስጣዊ ጥንካሬያችንን በማጎልበት ረገድ በቅድሚያ በውስጣችን የቅራኔ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ፣ የልማት፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማስወገድ መንግሥት እና ህዝብ በጋራ መስራት አለባቸው። አሁን ላይ እዚህም እዚያም የሚታዩ ጊዜያዊ ያለመረጋጋት ችግሮች ቢኖሩም፣ በምንኖርበት የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ካሉ አገራት ጋር በተነፃፃሪ ሲታይ አሁንም ድረስ ሰላሟን ያረጋገጠች አገር ኢትዮጵያ ናት።
ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር ዛሬ እየገነባችው ያለው ግንኙነት የጥንቱን ታሪኳን በመተረክ ሳይሆን የአሁኑ ትውልድ እየሠራው ባለው ተጨባጭ ገድል ላይ የተመሰረተ ነው። ይህ በመሆኑ፣ ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ በበለጸጉ አገራት የምትፈልገው እንደቀድሞው ዘመን በእርዳታ ሰጪነትና ተቀባይነት ስሜት ሳይሆን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን በአጋርነት ለመፈጸም ነው። የምሥራቁም ይሁን የምዕራቡ፣ የበለፀገውም ይሁን በማደግ ላይ ያለው ህዝብ ሁሉ ዓይን የሚያርፍባት ተፈላጊ አገር ሆናለች። ይህ የውሥጣዊ ጥንካሬያችን ውጤት መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ አካባቢዎች ያጋጠመንን ያለመረጋጋት ችግር ትውልዱ በፍጥነት ሊያስቆመው የሚገባ ነው። ማንኛውም ችግር ሊፈታ የሚችለው በሰለጠነ አካሄድ፣ በመወያየትና በመመካከር እንጂ በሁከትና ብጥብጥ ሊሆን እንደማይችል መገንዘብ ያስፈልጋል። ይህ በማድረግም በዓለም ላይ ያለንን ተሰሚነት ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ እንችላለን፡፡ ይገባልም፡፡
ሰሞኑን የሦስት ሃገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል፡፡ የአሜሪካ፣ሩስያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፡፡ እነዚህ ሃገሮች ከሃገራችን ጋር በንግድና ኢንቨስትመንትን፣ በሰላምና ጸጥታ ...አብረው ለመስራት ፍላጎታቸውን አሳይተዋል፡፡ ለፀረ ድህነት ትግሉ አሜሪካ ድጋፍ ሠጥታለች፡፡ ሩስያ ብድር ሰርዛለች፡፡የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስም ንግድና ኢንቨስትመንት በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላት አሳይታለች፡፡ይህ ሁሉ የጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ውጤት ነው፡፡እነዚህ ሃገሮች የመጡበት ወቅት ሃገራችን በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በአለችበት ወቅት መሆኑ ሲታይ ደግሞ ምን ያህል ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ እየተሠራ እንዳለ መገንዘብ ይቻላል፡፡
በሌሎች ሃገሮች የውስጥ ጉዳይ ‹‹እኔ ያልኩት›› ካልተገበራችሁ ብላ ጫና በመፍጠር የምትታወቀው አሜሪካ እንኳ በሃገራችን የውስጥ ጉዳይ ላይ ለመፈትፈት ፍላጎት አላሳየችም፡፡ምክንያቱም የመንግሥትንና የሃገሪቱን ግልጽ አቋም ስለምትገነዘብ ነው፡፡በሃገራችን ሁከት እንዲኖር በውጭ ሃገራት ሆነው የሚሠሩ ሃይሎች አሉባልታም መና ያስቀረ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡
የሃገራችን የሰሞኑ የተሳካ ዲፕሎማሲያዊ ድል እንዲሁም ለህዝቦች ሠላም፣ ልማትና ብልጽግና መረጋገጥ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ዋነኛ ተዋናይ መሆን የተቻለው በቅድሚያ የውስጥ ሠላም ለማረጋገጥ እና በተገኘው ሠላም አማካኝነትም ለእድገትና ብልጽግና መስራት በመቻሉ ነው። ስለዚህ ይህንን ጥረት አጠናክሮ በማስቀጠል የዲፕሎማሲው ድልም ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ ይገባል፡፡ይቻላልም፡፡ ለዚህ ደግሞ የሃገር ውስጥ ችግሮቻችን በውይይት እና ሰላማዊ በመሆኑ መልኩ የመፍታት ባህል ማዳበር አለብን፡፡ ውስጣዊ ጥንካሬያችን የፈጠረልንን ድሎች ለማስቀጠል የምንችለው በዚሁ መንገድ ነውና፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

አዲስ አበባ፡- ‹‹አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የኢህአዴግ አራቱም ብሄራዊ ድርጅቶች ሊቀመናብርት በጉዳዩ ላይ አስተያየት ሰጥተውና ተስማምተው የጋራ ውሳኔ ላይ በመድረሳቸው ጸድቋል›› ሲሉ የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ገለጹ፡፡ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ዛሬ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ከትናንት በስቲያ በጽህፈት ቤታቸው ከጋዜጣው ሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፤ የአዋጁ መጽደቅ የአራቱም ብሄራዊ ድርጅቶች የጋራ አቋም ነው፡፡ በተጨማሪም እንደግንባሩ ደግሞ የሥራ አስፈጻሚው ውሳኔና አቋምም ነው፡፡
በአዋጁ መጽደቅ ላይ ምንም ግራ የሚያጋባ ጉዳይ አለመኖሩን የተናገሩት አቶ ሽፈራው፣ አዋጁ ከመጽደቁ አስቀድሞ ገና በመጀመሪያው ላይ አፈ ጉባኤው ከ547ቱ የምክር ቤት አባላት መካከል አራት ሰዎች በህይወት አለመኖራቸውን፤ አራቱ ደግሞ በተለያየ ምክንያት በአገር አለመገኘታቸውንና በዕለቱ 490 ሰዎች መገኘታቸውን በመግለጽ ስብሰባውን ያስጀመሩት ይሄዳሉ:: ምልዓተ ጉባኤው መሟላቱን አረጋግጠው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ይህንንም በዕለቱ የተገኙት የመገናኛ ብዙኃን መስማታቸውን ገልጸዋል፡፡ ኃላፊው፣ በየትኛውም ስሌት ለአዋጁ መጽደቅ በቂ ድጋፍ መገኘቱን ጠቅሰው፤ ድምፅ ሲቆጠር ግን ቆጣሪዎች የፈጠሩት ስህተት መኖሩን አልሸሸጉም፡፡
የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባውን ዛሬ እንደሚጀምር የተናገሩት አቶ ሽፈራው፤ ከያዛቸው አጀንዳዎች መካከል በዋናነት ከአራቱም ብሄራዊ ድርጅቶች የሚቀርቡትን ሪፖርቶች የሚመለከተው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አገሪቱ ባለፉት ጊዜያት የተለያዩ ፈተናዎች እያጋጠሟት እንደመሆኑ ለዚህም መነሻው ምንድነው በማለት ፍተሻ ተደርጎ መፍትሔ እንደሚቀመጥም አስረድተዋል፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ባለፉት ወራት ይህን ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ ሲደረግ ነበር፡፡ ድርጅቱ ጊዜ ወስዶ ከታኅሣሥ 3 እስከ 20 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ታሪካዊ የሚባል ውይይት አድርጓል፡፡ መርህ አልባ ጉድኝት መስፈኑ፤ አድርባይነት መንገሡ ተገምግሟል፡፡ ይህም በትግል ይፈታ ነበር ሲል አምኗል፡፡
በተለያየ መንገድ ህግ የተላለፉ አካላትን በይቅርታ በመልቀቅ ዴሞክራሲውን ለማስፋት ጥረት መደረጉን ኃላፊው አመልክተዋል፡፡ ‹‹ይህ ሲደረግ ግን በማንም ጫናና ግፊት ሳይሆን ለዓላማችንና ለመርሐግብራችን ስኬት ስንል ነው›› በማለትም አስረድተዋል፡፡
ከኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ጋር የተደረገውን ሙሉ ቃለ ምልልስ በነገው ዕትማችን ፖለቲካ ገጽ እናቀርባለን፡፡

አስቴር ኤልያስ

 

 

Published in የሀገር ውስጥ

አዲስ አበባ ፦መደበኛ ላልሆነ ንግድ የሚያገለግሉ 45 ቦታዎች መለየቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የስምንት ወራት አፈጻጸምን በተመለከተ ትናንትና መግለጫ ሰጥቷል። የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዳምጤ አበበ እንደገለጹት፤ መደበኛ ባልሆነ የንግድ እንቅስቃሴዎችን መልክ ለማስያዝ በተደረገው ጥረት በከተማዋ የሚገኙ 45 ቦታዎች ተለይተዋል። በቦታዎቹ ላይ የንግድ ስርዓት የሚያከናውኑ ተጠቃሚዎችን የሽግግር ጊዜ ፈቃድ ሰርተፍኬት እንዲዘጋጅላቸው ተደርጓል።
መደበኛ ባልሆነ የንግድ ሥራ ውስጥ ተሰማርተዋል ተብለው የሚገመቱ 40 ሺ ሰዎች እንደሚኖሩ የገለጹት አቶ ዳምጤ፤ እያንዳንዱን በመመዝገብ በንግድ ስርዓቱ እንዲታቀፉ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አስታውቀዋል። በአሥሩም ክፍለከተሞች የሚገኙ 20 ሺ የሚጠጉ መደበኛ ያልሆኑ የንግድ ተሳታፊዎች ምዝገባ መካሄዱንም ተናግረዋል።
በቀጣይም መደበኛ ያልሆኑ ነጋዴዎችን የመመዝገብ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል። በምዝገባው የተካተቱትም በተዘጋጁት ቦታዎች ላይ በህጋዊ መንገድ እንዲነግዱ ዕድል መፍጠር የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል። በተለዩ ቦታዎች ላይ የሚደረገው የንግድ እንቅስቃሴ ለነጋዴዎች ከሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ የእራሱ የሆነ ድርሻ እንደሚያበረክት ይጠበቃል።
ከዋጋ ግሽበት ጋር በተያያዘት የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የየካቲት ወርን መረጃ ይፋ ባደረገበት ወቅት የወሩ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 15 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱን አስታውቋል። የዋጋ ግሽበቱ ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር የሁለት ነጥብ አምስት በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም መረጃው ያመለክታል።
ኤጀንሲው ባስተላለፈው መረጃ መሰረት፤ በየካቲት ወር በእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች መጠነኛ ቅናሽ ቢያሳዩም ሌሎች የምግብ ምርቶች በአብዛኛዎቹ ዋጋ ጨምሯል። በተለይ የጥራጥሬ፣ የአትክልትና የፍራፍሬ ዋጋ ጭማሪ አሳይቷል። በርበሬ እና የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች ዋጋ በአንድ ወር ውስጥ ባልተለመደ መልኩ ከ50 በመቶ በላይ ጭማሪ አሳይተዋል። ይህም ለአጠቃላይ ምርቶች የዋጋ ግሽበት መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። በተጨማሪም ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች፣ አልባሳትና ጫማ፣ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች፣ የኃይል ፍጆታዎች፣ የቤት ውስጥ መገልገያዎች፣ የጤና ወጪ እንዲሁም በሆቴሎች የሚቀርቡ ምግቦችና መጠጦች ላይ ጭማሪ መከሰቱ ለዋጋ ግሽበቱ መጨመር አስተዋጽኦ ካደረጉ መካከል ይገኙበታል።

ጌትነት ተስፋማርያም

Published in የሀገር ውስጥ

በአገሪቷ የሚገነቡ ፋብሪካዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ጠንካራ የሥራ ባህልን የተላበሰ ሠራተኛ ያስፈልጋቸዋል። በአብዛኛው ፋብሪካዎች ውስጥ ግን ከሥራ የሚቀሩ፣ የሚያረፍዱ እና ሥራ ይዘው የሚያዘገዩ ሠራተኞች እንደሚገኙ ከድርጅቶቹ እንደቅሬታ ይነሳል። ይህም በምርት መቀነስ እና በትርፋማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል። «በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ» እንዲሉ ደግሞ የጨርቃጨርቅ ምርት ላይ የተሰማሩ ፋብሪካዎች ከደካማ የሥራ ባህል በተጨማሪ የግብዓት እጥረት ያጋጥማቸዋል።
በተለይ የጨርቃጨርቅ ምርቶች ወጪ ንግድ በማሳደግ ረገድ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ በሚገኘው አይካ አዲስ ቴክስታይል ፋብሪካ ላይ ካለፉት አራት ወራት ጀምሮ የድንጋይ ከሰል ግብዓት እጥረት እየፈተነው መሆኑን የድርጅቱ መረጃ ያመላክታል። ከጨርቃጨርቅ ምርቶች ግብዓት ጋር ተያይዞ እጥረት በማጋጠሙም የገበያ ትዕዛዞቹን በወቅቱ ማድረስ አለመቻሉ በአገር አቀፍ ደረጃ የዘርፉን የወጪ ንግድ መቀዛቀዝ ላይ ጥሎታል። ያሳደረው ተጽዕኖም ከፍተኛ መሆኑ ድርጅቱ ይገልፃል።
የአይካ አዲስ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ገቢና ወጪ ንግድ ሎጂስቲክ ማናጀር አቶ ቢንያም አብረሃም እንደሚናገሩት፤ ፋብሪካው ባለፉት ስድስት ወራት ከተቀባዮቹ ፍላጎት ጋር የተጣጣም ምርት ማቅረብ አልቻለም። ችግሮቹ አንድም ከግብዓት በሌላም በኩል ከሥራ ባህል ጋር የተያያዙ ናቸው።
ፋብሪካው የሀገሪቷን የዘርፉን ወጪ ንግድ ከግማሽ በላይ ድርሻ የሚይዝ ነው። ነገር ግን የሥራ ባህላቸው ያደገና በሰዓቱ ምርት ለማድረስ የሚያስችሉ ሠራተኞችን ከገበያው ማግኘት አዳግቶታል። የሠራተኞቹ የሥራ ተነሳሽነት ከዚህ ቀደም ካለው የተሻለ ቢሆንም በወጪ ንግዱ ላይ በስፋት ለመሳተፍ ቢፈልግም አሁንም ደካማ አሰራር ይታይበታል። በቱርክ ባለሃብቶች የተቋቋመው አይካ አዲስ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ አገር ውስጥ እስከተገነባ ድረስ የኢትዮጵያውያንም ሃብት በመሆኑ ውጤታማ እንዲሆን የሠራተኞችን የሥራ ባህል ለማዳበር ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አቶ ቢንያም ይናገራሉ።
አይካ አዲስ ለሚያመርታቸው ጨርቃጨርቅ ማቅለሚያ ግብዓትነት የሚያገለግለው የድንጋይ ከሰል እጥረት ማጋጠሙ ባለፉት ስድስት ወራት የምርት መቀነስ እንዲገጥመው ዋነኛ ምክንያት ሆኗል። በግብዓት እጥረቱ ምክንያትም በውጭ አገራት ለሚገኙ ደንበኞቹ ማድረስ የነበረበትን ምርት በሚፈለገው ደረጃ ማቅረብ አልተቻለም። አይካ አዲስ በቀን 80 ቶን የድንጋይ ከሰል ምርት ያስፈልገዋል። የድንጋይ ከሰል ምርቱን ከአገር ውስጥ አምራቾች የሚረከብ ቢሆንም፤ የምርት እጥረት በመፈጠሩ በቂ ማቅለሚያ ማግኘት አልቻለም። ከክር ጀምሮ እስከ መጨረሻው የጨርቃጨርቅ ምርት ድረስ የተለያዩ ህብረ ቀለማትን ለመፍጠር የድንጋይ ከሰል እና ጨው አስፈላጊነታቸው ከፍተኛ ቢሆንም በቂ ግብዓት በወቅቱና በሚፈለገው መጠን አለመገኘቱ ለዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ እንቅፋት ሆኖ መቀጠሉን አቶ ቢንያም ይገልጻሉ።
«ፋብሪካው አምርቶ ገዢዎችን በማፈላለግ የሚሸጥ ሳይሆን በትዕዛዝ የቀረቡለትን የሚያመርት ነው» የሚሉት አቶ ቢንያም፤ በግብዓት እጥረት ምርት በወቅቱ ያልደረሰላቸው ደምበኞች በተለይም የጀርመን መዳረሻዎች በቀጣይ ትዕዛዝ ለመስጠት ያላቸው ፍላጎት ይቀንሳል። በመሆኑም ድርጅቱ ወደኪሳራ እንዳያመራ አቅርቦቱን መንግሥት እንዲያሟላ የሚያደርገውን ጥረት ማጠናከር እንደሚገባው ያስረዳሉ።
በኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ባንቲሁን ገሰሰ እንደገለጹት፤ የውጭ ድርጅቶች የእራሳቸውን እውቀት እና ልምድ ይዘው ይመጣሉ። በቂ አቅምም አላቸው። ነገር ግን አገር ውስጥ ጨርቃጨርቅ በሚያመርቱበት ወቅት የሚፈልጉትን ያህል ባለሙያ ላያገኙ ይችላሉ። የሰው ኃይሉን ለሥራ ያለው አመለካከት እና በቂ እውቀት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚፈታ ሳይሆን በሂደት የሚዳብር ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ክህሎት በሂደት እየተሻሻለ የሚመጣ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ተወዳዳሪ ምርት ማዘጋጀት የሚችል የሰው ኃይል ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጠረ እንደሚገኝ ይናገራሉ።
በተለያዩ ጊዜያት በሚሰጡ አጫጭር ስልጠናዎች አማካኝነትም ቀደም ካሉ ዓመታትም የተሻለ የሥራ ዕውቀትና የሥራ ባህል እየዳበረ መምጣቱን መመልከት ይቻላል። ችግሩ ግን የሰለጠኑ ባለሙያዎች የደመወዝ እና የተለያዩ ጥቅማጥቅሞች ፍለጋ ከአንዱ ፋብሪካ ወደሌላው የሚያደርጉት ፍልሰት ነው። በመሆኑም ባለሙያዎቹን ጠብቆ ምርታማነቱን ለማስቀጠል ድርጅቶቹ በየጊዜው የእራሳቸውን የማትጊያ መንገዶች መጠቀም እንደሚኖርባቸው አቶ ባንቲሁን ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ባንቲሁን ማብራሪያ ከሆነ፤ አይካ አዲስ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ በሌላ በኩል ያሉበት የግብዓት እጥረት የተፈጠረው በትስስር ክፍተት ምክንያት ነው። በተለይ በድንጋይ ከሰል ምርት አቅርቦት ከባለሃብቶች ወደ ሥራ አጥ ወጣቶች በመሸጋገሩ ከፋብሪካው ጋር በቂ ግንኙነት አልተደረገበትም። የግብዓት ችግሩን ለመቅረፍ አዲስ አምራች የሆኑት ወጣቶችን ከፋብሪካዎች ጋር በማስተሳሰር ምርት እንዲያቀርቡ እየተደረገ ይገኛል። የግብዓቱ ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ሥራ በመከናወኑ የአምራቾች የማቅለሚያ ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚፈታ ይጠበቃል። በየዕለቱ በአምራቾች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን እየመዘገቡ መረጃ የሚያቀርቡ ባለሙያዎችም በመመደባቸው ከሥር ከሥሩ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል አሰራር ተዘርግቷል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የጥናትና ክትትል ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ ዘሪሁን አበበ በበኩላቸው፤ የአይካ አዲስ ዋነኛው ችግር የግብዓት እጥረት በተለይም የድንጋይ ከሰል ግብዓት ነው። ፋብሪካው ከኢፌዴሪ ብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን የያዮ ማዳበሪያ ድንጋይ ከሰል ልማት ፕሮጀክት የድንጋይ ከሰሉን ይረከብ ነበር። በአሁኑ ወቅት ከያዮ ማምረቻ 50 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ወጣቶች ተደራጅተው እንዲያለሙ በመፈቀዱ ምርቱን ለፋብሪካው እንዲያቀርቡ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል ጌዶ አካባቢ ሌሎች ወጣቶች ተደራጅተው 100 ቶን ድንጋይ ከሰል ለማምረት በሂደት ላይ በመሆናቸው ለተለያዩ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ግብዓቱም ማቅረብ የሚያስችል ዕድል እየሰፋ መሄዱን ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ዘሪሁን ገለጻ፤ አይካ አዲስ ነባር ፋብሪካ በመሆኑ የልምድ ማነስ እና ደካማ የሥራ ባህል ያላቸው ሠራተኞች በብዛት የሉትም። እንደውም ችግሩ በአዳዲስ ፋብሪካዎች ላይ የጎላ በመሆኑ የተለያዩ የማበረታቻ መንገዶችን በሠራተኞች ላይ መጠቀም ያስፈልጋል። ማትጊያዎች በብዙ ቁጥርም የኢንዱስትሪውን የሥራ ባህል ማሳደግ ይቻላል።

ዜና ሐተታ
ጌትነት ተስፋማርያም

Published in የሀገር ውስጥ

ከሲኤምሲ ወደ አያት እየተጓዘኩ ሳለሁ ከፊት ለፊቴ ያሉ የትምህርት ቤት የደምብ ልብስ የለበሱ ሦስት ተማሪዎች ሞቅ ያለ ወሬ ይዘዋል። ትምህርት ቤት ከመግባታቸው በፊት መድኃኒታቸውን መግዛት እንዳለባቸው እያወሩ ነው:: አንዷ ተማሪ 50 ብር ከቦርሳዋ አውጥታ ፊት ለፊቷ ከሚገኘው መድኃኒት መደብር ገባች። ከገዛችው መድኃኒት ውስጥ ለሦስቱም ጓደኞቿ አንድ አንድ አነስተኛ እሽግ አከፋፈለቻቸው:: 

ሦስቱም ተማሪዎች በአንድነት ከእሽጉ ያወጡትን አምፒሲሊን መሰል መድኃኒት የቻሉትን ያህል ፍሬ ከማሸጊያው ላይ እየፈለቀቁ ወደአፋቸው ላኩት:: ከዚያ በኋላ ራሳቸውን መቆጣጠር እስኪሳናቸው ድረስ ተንገዳገዱና ተቀመጡ:: ሌሎች አልፎ ሂያጅ ተማሪዎች ግን እነርሱን እያዩ ይሳሳቃሉ:: መድኃኒቱን ለማወቅ ያለኝ ፍላጎት ጨመረ:: መድኃኒቱን ወደገዙበት መድኃኒት ቤት ሄጄ ሳጣራ የህመም ማስታገሻ መድኃኒት ቢሆንም የማነቃቃት ባህሪ ያለውና ሱስ የሚያስይዝ እንክብል መሆኑንና ተማሪዎች በብዛት እንደሚጠቀሙት ተረዳሁ::
ከመድኃኒት ወሳጆቹ መካከል ሐያት (ስሟ የተቀየረ) ትገኝበታለች:: አዲስ አበባ ሲኤምሲ አካባቢ በሚገኘው ዲቦራ ትምህርት ቤት የአስረኛ ክፍል ተማሪ ናት:: ዕድሜዋ በግምት 17 ሰባት ይሆናል:: በየቀኑ አዕምሮዋ አምጪ አምጪ የሚላትን መድኃኒት ካልወሰደች ድብርትና ድካም ይጫጫ ናታል፤ አዕምሮዋ ይረበሻል:: ምክንያቱም መድሃኒቱን በተደጋጋሚ በመውሰዷ ልክ እንደ ጫት እና ሲጋራ ሱስ እንደሆነባት ትናገራለች። እሱን ካላገኘች እረፍት አይሰጣትም:: ቤተሰቦቿ ስለ ጉዳዩ ስለማያ ውቁ ሁልጊዜም ደህና እንደሆነች ያስባሉ:: እሷም ችግሯን ለመናገር አልደፈ ረችም።
ከመድኃኒቱ ጋር የተዋወቁት የዛሬ አራት ወር ገደማ እንደሆነ ትናገራለች። የትምህርት ቤት ጓደኛዋ ዶናዶል የሚባል መድኃኒት እንዳለ እና እንደሚ ያነቃቃ ከሰማች በኋላ ለመሞከር ትወስናለች:: ወዲያውም መድኃኒቱን ገዝተው አምስት አምስቱን በአንድ ጊዜ ይውጡታል:: ብዙም ሳይቆዩ ሁለቱም ተዝለፍልፈው መውደቃቸውን ታስታውሳለች:: በትምህርት ቤቱ አካባቢ የነበሩ ወጣቶች በእጃቸው ላይ የነበረውን መድኃኒት ቀድሞም ስለሚ ያውቁት ደጋግፈው አንድ ጥግ ያሳርፏቸውና ምንም እንዳል ተፈጠረ «የመጀመሪያችሁ ስለሆነ ነው አይዟችሁት ለምዱታላችሁ» በሚል አበረታተዋቸው በዚህ የተጀመረው ሱስ አሁን ላይ በየቀኑ ሦስት እና አራት የትራማዶል (ዶናዶል) እንክብሎችን እስከማስዋጥ እንዳደረሳት ትናገራለች::
በየቀኑም ከደብተር ቦርሳዋ ውስጥ በምትይ ዘው ትራማዶል የተሰኘውን መድኃኒት በትምህርት ቤት ምሳ ሰዓት ላይ ሦስት እንክብሎችን በአንዴ እንደምትውጥ ትናገራለች:: ማታም እንዲሁ ከቤተሰቦቿ ተደብቃ ትደግመዋለች:: ይህ በየቀኑ የሚደረግ ልምድ ወደሱስነት እንደተቀየረ ብትረዳም ለመተው ተቸግራለች:: በየቀኑ ኪኒኑን መውሰድ ሱስ ቢሆንባትም እስከ መቼ እንደዚህ ሆና እንደምትቀጥል ግን ለእራሷም ግራ ተጋብታለች::
«አሁን አሁን ሱስ አስያዡን ከየትኛውም መድኃኒት መደብር ሸምቶ በየቀኑ የሚቅመው ተማሪ ተበራክቷል:: እኔ ብቻ አይደለሁም አብዛኛው ተማሪዎች ይወስዱታል» በማለት ችግሩ የእርሷ ብቻ ሳይሆን የአብዛኛው የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች እንደሆነ አስተውላለች:: በዚሁ መድኃኒት ባለፈው ወር ብቻ በአንድ ጊዜ አስር ተማሪዎች እራሳቸውን ስተው መውደቃቸውንም ታስታውሳለች:: መድኃኒቱ በ10 እና 15 ብር በየፋርማሲው ያለማዘዣ የሚገኝ በመሆኑ የአራተኛ ክፍል ተማሪዎች ሳይቀሩ እየተጠቀሙት በመሆኑ አንድ መፍትሄ እንዲፈለግለት ትማፀናለች::
እኔም የሻጮቹ ያለማዘዣ እውነት መሆኑን ለማጣራት በአካባቢው ከሚገኘው አንድ የመድኃኒት መደብር አመራሁ:: ያለምንም የሐኪም ማስረጃ ይህንን ሱስ አስያዥ መድኃኒት በ15 ብር ገዝቼ ደረሰኝ ተቀበልኩ:: ከገዛሁ በኋላ ግን ፋርማሲ ባለሙያዋን እንዴት ያለ ማዘዣ ትሸጫለሽ? ብላት መልሷ አንገት ማቀርቀር ብቻ ሆነ:: ጥፋት እንደሆነ ብታውቀውም ገንዘብ ነውና በየቀኑ ለጠየቃት ሁሉ እንደምትቸበችበው ተረዳሁ:: ጉዳዩን ይዤ ወደ ተቆጣጣሪው ባለስልጣን አመራሁ::
ትራማዶል ወይም በአምራች ስሙ ዶናዶል የተባለው የመድኃኒት አይነት ሰውነት ውስጥ ከገባ በኋላ ወደ «ሞርፊንነት» የሚቀየር መድኃኒት መሆኑን የገለጹልኝ የአዲስ አበባ_የምግብ፣ የመድኃ ኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደ ርና_ቁጥ ጥር_ባለስልጣን ፋርማሲስት አቶ ይመር ሁሴን ናቸው:: እንደ እርሳቸው ገለፃ መድኃኒቱ ያለ የሐኪም ማስረጃ መሸጥ የሌለበት ቢሆንም በየመ ድኃኒት መደብሩ በግላጭ እንደሚቸበቸብ ይገልጻሉ::
መድኃኒቱ ሱስ ከማስያዙ በላይ ተማሪዎቹ ላይ የጉበት እና አደገኛ የመተንፈሻ አካላት በሽታ የማስከተል አቅም እንዳለው የሚናገሩት አቶ ይመር፤ መሸጥ ካለበትም በሐኪም የታዘዘለት ታካሚ ብቻ ነው:: ነገር ግን ትክክለኛ አሰራር ተከትለው የሚሸጡ መደብሮች ቁጥራቸው አነስተኛ በመሆኑ በየቦታው እየተቸበቸበ ይገኛል:: ከሚታሰበው በላይ በርካታ ተማሪዎች እየወሰዱት ያለ መድኃኒት ሆኗል:: መስሪያ ቤታቸው ጉዳዩን ተከታትሎ እርምጃ ለመውሰድ ያለው አቅም እና ክትትል ደካማ በመሆኑ በርካታ መድኃኒቶች ያለማዘዣ በመሸጥ ላይ መሆኑንም ታዝበዋል:: በመሆኑም መድኃኒት መደብሮች ያለሐኪም ማስ ረጃ የትኛውንም ዓይነት መድኃኒት እንዳይሸጡ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል::
የስነ አዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት አስመረት ወልደብርሃን (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ መድኃኒቱ «ኦፖይድ» የሚባል ሱስ አምጪ ንጥረ ነገር አለው። መድኃኒቱ ለካንሰር ህመም፣ ለመገጣጠሚያ በሽታ፣ ከቀዶ ህክምና በኋላ እና ለሌሎችም ህመም ሲያጋጥም ስቃይን ለመቀነስ ይረዳል። በአግባቡ ለህክምና ጥቅም ሲውል በአግባቡ ይሰራል። ነገር ግን ተማሪዎች በዘፈቀደ ሲወስዱት አካላዊ እና ስነልቦናዊ ጉዳት የማስከተል አቅም እንዳለው ይናገራሉ።
በመድኃኒቱ ምክንያት ሱስ ውስጥ የገቡ ወጣቶችም ልክ እንደማንኛውም የሱስ ዓይነት አስፈላጊው የሥነአዕምሮ ህክምና ያስፈልጋቸዋል። ከሱሱ መላቀቅ ከፈለጉም የሥነልቦና ሐኪሞች ጋር ቀርበው ተከታታይ ህክምና ማድረግ እንደሚገ ባቸው ይመክራሉ። መድኃኒቱን በሚቋርጥበት ወቅት ምን ችግር ይደርስብኛል? ብለው ለሚሰጉም በሚሰጠው ህክምና አማካኝነት በጊዜ ሂደቶች ከሱስ ለመላቀቅ የሚያግዙ መድኃኒቶችንም ያገኛሉ። ለአብነት ዶናዶልን ሲያቋርጡ የእንቅልፍ እጦት ካጋጠማቸው በምትኩ የእንቅልፍ መድኃኒት፤ ድብርት ካጋጠማቸው ደግሞ ዘና የሚያደርጉ ጤነኛ መንገዶችን ለአማራጭነት ከሐኪሞች ማግኘት ይችላሉ። በመሆኑም የሱስ ተመራጭ የለውምና ተማሪዎቹ ላይ የሚታየውን ችግር ተቀራርቦ መቅረፍ እንደሚቻል ያሳስባሉ።
ጉዳዩ የሚመለከተው የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ስለጉዳዩ ምንነት እና ስለሱስ አስያዡ መድኃኒት እና ስለተማሪዎች ግንኙነት ባለማወቃ ቸው መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም::

ዜና ሐተታ
ጌትነት ተስፋማርያም

Published in የሀገር ውስጥ

ትምህርት ቤቶች የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ እንዲወጡ ከሚያደርጓቸው መሰረተ ልማቶቻቸው አንዱና ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፈው ቤተ መጽሐፍት ነው፡፡ ቤተ መጽሐፍት ደግሞ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ በአግባቡ ሊደራጅና ተማሪዎች የሚፈልጉትን መጽሐፍት መያዝ ይኖርበታል፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በየትምህርት ቤቶች የሚገኙ ቤተ መጻሕፍት በዚህ መልኩ የተደራጁ ናቸው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ይህ እውነት በታችኛው የትምህርት ደረጃ ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም የዘወትር አቤቱታ መሆኑ እውን ነው፡፡ ታዲያ ዛሬ ዓለም ከደረሰበት የቴክኖሎጂ ደረጃ አንጻር ሲታይ ይህ አሰራር ሊቀየር እንደሚገባው እሙን ነው፡፡ ምክንያቱም የቤተ መጽሐፍት ተጠቃሚው ፍላጎት በየጊዜው እያደገ እንደመሆኑ በተገቢው መጻሕፍት ያልተደራጁ ቤተ መጽሐፍት ይዞ ከመቀመጥ ባለፈ ተጠቃሚው በቀላሉ ሊያገኛቸው በሚችልበት ቴክኖሎጂ ታግዞ ማደራጀት ያስፈልጋል፡፡ ይሄን የተረዳውም የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል ብሔራዊ ዲጂታል ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት እውን አድርጓል፡፡
“አሁን ላይ የተወሰነ መሻሻል ቢታይም፤ እኛ ድሮ ተማሪ እያለን አንድ መጽሐፍት ለአርባና ሃምሳ ተማሪ አገልግሎት ይሰጥ ስለነበር ወረፋ ይዘን ነበር የምንገለገለው”፣ የሚሉት የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ሳህለማርያም ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ የዲጂታል ቤተመጽሐፍቱ እውን መሆን መረጃን በወረቀት ከማድረስ ይልቅ በሶፍት ኮፒ ለማድረስ፤ በወረቀት ያለን አንድ መጽሐፍ በአንድ ጊዜ አንድ ሰው ይዞ ሲጠቀም ሌላው የማያገኝበትን አሰራር በማስቀረትም አንድን መጽሐፍ በአንድ ጊዜ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች እንዲያነብቡት የሚያስችል ነው፡፡
እንደ አቶ ተሾመ ገለጻ፤ ዲጂታል ቤተ መጽሐፍቱ በዋናነት ለዩኒቨርሲቲዎች፣ ለምርምር ተቋማት፣ ለኢንዱስትሪዎችና ሌሎች ተቋማት ጥቅም የሚሰጥ ሲሆን፤ እነዚህ ተቋማት የሚፈልጓቸውን መረጃዎች ከድረ ገጽ ላይ በማውረድ ወይም እዛው ላይ በማየት የሚያገኙበት አሰራር ነው፡፡ በመሆኑም ተማሪዎች፣ ተመራማሪዎችና ሌሎችም የሚፈልጉትን መረጃ በሚፈልጉበት ቦታ ሆነው በቀላሉ እንዲያገኙ፣ ቴክኖሎጂዎችን እንዲረዱና ለቴክኖሎጂ ሽግግሩ መፋጠንም የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ የሚያስችል ነው፡፡ ለተማሪዎች ብቻ ሳይሆን መምህራንም የሚፈልጉትን ማጣቀሻ መጽሐፍት በቀላሉ እንዲያገኙ በማድረግ ከፍተኛ ድጋፍ ይሰጣል፤ የመማር ማስተማር ሂደቱንም ፈጣንና ቀልጣፋ ያደርገዋል፡፡
የመረጃ ማዕከሉ ከተቋቋመ ገና አጭር ጊዜው ቢሆንም ሰፊ ስራ እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ተሾመ፤ ለአብነትም በዩኒቨርሲቲዎች የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ስራዎች ወደ አንድ የመረጃ ቋት የሚገቡበት እድል እንዲፈጠር በማድረግ የጥናትና ምርምር ስራዎች በምን ርዕሰ ጉዳይ፣ በማን እና መቼ ተከናወኑ የሚለው እንዲታወቅ በማስቻል ተመሳሳይ ወይም ኮፒ ስራዎች እንዳይሰሩና አላስፈላጊ ድግግሞሽ እንዳይኖር ለማስቻል ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በማዕከል ቴክኒካል አማካሪ የሆኑት አቶ ዮዳሄ ዓርአያ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ የወረቀት መረጃዎችን ይዞ በሚገኝ ቤተ መጽሐፍት የመጽሐፍ እጥረት ሲኖር አንድ መጽሐፍ አንድ ተማሪ ከያዘ ሌሎች መጽሐፉን የሚፈልጉ ተማሪዎች ይሄን መጽሐፍ ማግኘት ስለማይችሉ የግድ እርሱ እስኪመልስ መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ ሂደት አንድን መጽሐፍ በቀላሉ 40 ተማሪ የሚፈልገው ቢሆን የሚፈጥረውን መጉላላትና የሚፈልጉትን መረጃ የማግኘት ችግር መገመት ይቻላል፡፡ አሁን ግን ዓለም ካለበት የቴክኖሎጂ ደረጃ አኳያ አንድ ተማሪ የትም ቦታ ሆኖ መጽሐፍ በሞባይል ስልኩ ወይም በላፕቶፕ ኮምፒዩተሩ ላይ ማንበብ ሊፈልግ ይችላል፡፡ የዲጂታል ላይብረሪ እውን መሆን ደግሞ ተማሪዎች በወረቀት ላይ ያለን መረጃ ለማግኘት ከሚደርስባቸው መጉላላት እንዲላቀቁና በድረ ገጹ አማካኝነት የሚፈልጉትን መጽሐፍ ወይም ሌላ ሰነድ በሶፍት ኮፒ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ አንድን መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ ይዞ የመቀመጥን አሰራር፤ በዲጂታል ላይብረሪው የተለቀቀን አንድ መጽሐፍ አንድ ሚሊዮን ተማሪም ቢሆን በአንድ ጊዜ እንዲገለገልበት እድል የሚሰጥ ነው፡፡ ይሄን በመገንዘብም ዩኒቨርሲቲዎች የተለመደውን ቤተ መጽሕፍት ቀስ እያሉ ወደ ዲጂታል የመቀየር ስራ ጀምረዋል፡፡
የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከልም ባለፉት ሶስት አመታት በዚህ ዙሪያ እየሰራ ሲሆን፤ አሁን ላይ ተጠናቅቆ ወደስራ የገባው ዲጂታል ቤተ መጽሐፍትም በዋናነት ተደራሽነቱ ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እንዲሁም ማንኛውም ጥናትና ምርምር ለሚያደርግ ሰው የሚያገለግል ነው፡፡ በዚህ ዲጂታል ቤተ መጽሐፍት ውስጥ ወደ 57ሺ የሚጠጉ መጻሕፍት፣ ከ600ሺ በላይ የፓተንት መረጃዎች፣ ከሰባት ሺ በላይ የሕግ ሰነዶች፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ ጊዜ ሲሰሩ የነበሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች የዲዛይኖች እና ሌሎች የተለያዩ ሰነዶች አሉ፡፡ በቀጣይም የዲጂታል ቤተ መጽሐፍቱ ተደራሽነት በማሳደግ ለቴክኒክና ሙያ ተቋማት፣ ለሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች፣ ለመጀመሪያ ደረጃ እንዲሁም ለቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች የሚሆኑ መጽሐፍትን፣ ተንቀሳቃሽ ምስሎችንና ስዕሎችን የያዙ ሰነዶችን በማካተት በተተኪው ትውልድ ላይ የመስራት አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
እንደ አቶ ዮዳሄ ገለጻ፤ ዲጂታል ቤተ መጽሐፍቱ ኢንተርኔት ባለበት አካባቢ ሁሉ የሚሰራ ሲሆን፤ የኢንተርኔት መቋረጥ ቢያጋጥም ግን በሞባይል አፕሊኬሽን ወይም በኢንተርኔት አማካኝነት በሁለት መልኩ አገልግሎቱን ማግኘት ይቻላል፡፡ ይሄም የሞባይል አፕሊኬሽኑ ኢንተርኔት ባለበት ወቅት የሚፈልገውን የትምህርት መስክ መሰረታዊ ፓኬጅ በማውረድ ኢንተርኔት በሚጠፋበት ወቅት በፓኬጁ ውስጥ ያሉ በርካታ መጽሐፍትን መጠቀም የሚያስችለው ነው፡፡ ሁለተኛው ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን በኢንተርኔት (ኢትዮጵያን ኢዱኬሽናል ሪሰርች ኔትዎርክ) አማካኝነት ዲጂታል ቤተ መጽሐፍቱን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ሲሆን፤ እስካሁንም በ33 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ በቀጣይ ግን ከእነዚህ ሁለቱ መንገዶች ባለፈ ሌሎች የመድረሻ መንገዶች እየታሰቡ ሲሆን፤ መጽሐፍቱም በአግባቡ ተደራጅተው ተደራሽ እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ ከሰው ኃይል ጀምሮ እስከ ቴክኖሎጂ ያሉ ክፍተቶችን በመሙላትም ከተለያዩ አካላት ጋር በትብብር የሚሰራ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በተለያየ መልኩ ያገኟቸውንና የራሳቸው ብቻ የሆኑ መጽሐፍትን ጭምር የጋራ ላለማድረግና በሌሎች ምክንያቶች የዩኒቨርሲቲዎች በሚፈለገው ልክ ተባባሪ ያለመሆን አዝማሚያ አለ፡፡ ሆኖም ዩኒቨርሲቲዎች ያላቸው የመጽሐፍት ሀብት በማካፈል በጋራ የመስራትን ባህል ማዳበር ይኖርባቸዋል፡፡ እነዚህን በጋራ መጠቀም የሚያስችል አሰራርም ቢዘረጋ መልካም ነው፡፡
የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃዎችን ሰብስቦ፣ አደራጅቶ፣ ተንትኖና እሴት አክሎ ለመረጃ ተጠቃሚዎች የማሰራጨት ዓላማን ይዞ በ2004 በሕግ የተቋቋመው የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል፤ በ2006 በይፋ ስራ መጀመሩን የሚገልጹት የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍሰሃ ይታገሱ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ መረጃን መሰረት ያደረገ የፖሊሲ አወጣጥና ማርቀቅ ሂደት እንዲኖር ለፖሊሲ አውጪዎች መረጃዎች እንዲደርሱ ማድረግ፤ ለቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያግዙና እሴት የታከለባቸው መረጃዎችን ለዩኒቨርሲቲዎች፣ ለምርምር ተቋማት፣ ለተማሪዎችና ተመራማሪዎች የማሰራጨት ሥራን እያከናወነ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ለተግባሩ መሳካት ዕውን የሆነው የብሔራዊ የዲጂታል ቤተ መጻሕፍትም ከየትኛውም ምንጭ የሚገኙ መረጃዎችን በማደራጀትና በማከማቸት በኢንተርኔት አማካኝነት ለዩኒቨርሲቲዎች፣ ለተማሪዎችና ለተመራማሪዎች ተደራሽ የሚደረግበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አቶ ፍስሃ እንደሚናገሩት፤ በእስካሁኑ ሂደት የድረ ገጽና የአሰራር ማበልጸግ እንዲሁም የይዘት ማደራጀትና ማከማቸት ተግባራት ተከናው ነዋል፡፡ በዚህም በዓለም አቀፍ መመዘኛ በትምህርት ዘርፍነት የተጠቀሱ በማህበራዊም ሆነ በተፈጥሮ ሳይንስ መስኮች ከ25 በላይ በሚሆኑ መስኮች መጽሐፍቶች ያሉት ሲሆን፤ በጠቅላላው ወደ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ (መጽሐፍት፣ ጆርናሎች፣ የምርምር ውጤቶች) ይዘቶች በዲጂታል ላይብረሪ ውስጥ በኦን ላይን ተለቅቀዋል፡፡ ተጠቃሚው አንድም በድረ ገጹ ኦንላይን በማንበብ፤ በሌላም በኩል የሚፈልገውን መረጃ በነጻ አውርዶ መጠቀም ይችላል፡፡
ማንኛውም ሰው ኢንተርኔት ባለበት የኢትዮጵያ ክልል ሁሉ stic.gov.et ብሎ ቢገባ ሊያገኘው እንደሚችልም ታውቋል፡፡ በኢንተርኔት ኔትዎርክ የታቀፉ ዩኒቨርሲቲዎች ይሄንን ዲጂታል ቤተ መጽሐፍት ከኢንተርኔት ውጪ ሊያገኙት ይችላሉ፡፡ እውቀትና መጽሐፍት የሁሉምና ለሁሉም እንደመሆናቸውም ይህ ዲጂታል ቤተ መጽሐፍት ከመጽሐፍት፣ ከጆርናል አርቲክሎችና ከምርምር ውጤቶች ባለፈ ዝርዝር ዓለማአቀፍ የፈጠራ ዲዛይኖች ያሉበት በመሆኑ ለፈጠራ ባለሙያዎች እጅጉን ጠቃሚ ነው፡፡ በመሆኑም በታዳጊ አገሮች ከትምህርት ጥራት ጀምሮ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ያለው የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ በትምህርቱ ዘርፍ በዚህ መልኩ በዲጂታል ቤተመጻሕፍት በስፋት ለመጠቀም ከዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ሌሎች በቤተ መጻሕፍት ላይ ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር ለመስራት ማዕከሉ ፍላጎት ያለው በመሆኑ በትብብር ቢሰሩ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ጠቃሚ ይሆናል፡፡

ወንድወሰን ሽመልስ

Published in ማህበራዊ

       ኢህአዴግ ባለፉት ወራት በተከታታይ ማለት በሚያስችል መልኩ የአገሪቱን ሰላም ወደነበረበት ለመመለስ ደፋ ቀና ሲል መሰንበቱ ይታወቃል፡፡ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስም ራሱን ማየት የጀመረ ሲሆን፤ ከዚህ አኳያም ዋናው ችግሩ ‹‹የስልጣን እይታ ብልሽት ነው›› ሲልም ራሱን መገምገሙ አይዘነጋም፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥም ትልልቅ የሚባሉ ጉዳዮች ላይ መክሮ ወሳኔ ያስተላለፈ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል እስረኞች ይቅርታ ተደርጎላቸው እንዲለቀቁ መደረጉ እሙን ነው፡፡ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በትናንትናው እለትም ብሄራዊ ድርጅቶቹ የደረሱበትን ሪፖርት ለመገምገምና በሌሎች ጉዳዮች ላይም ለመምከር ስብሰባ መቀመጡ ይታወቃል፡፡ እነዚህንና ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክተን የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ድርጅቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያጋጠሙትን ክስተቶች በመመልከት ስርዓቱ አደጋ ላይ ነው ሲል አምኖ ችግሮቹን ለመፍታት መንቀሳቀሱ ይታወቃልና እንዴት ነበር የተመለከተው?
አቶ ሽፈራው፡- በ1993 ዓ.ም የተካሄደው የታድሶ እንቅስቃሴ ኢህአዴግ የሚከተለው ስርዓት ምንነትና የሚመራበት አቅጣጫ መስመር ምን እንደሆነ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ በዚህ ታህድሶ ጊዜ በግልጽ የተቀመጡ ጉዳዮች አሉ፡፡ አንዱ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊነት በዚህ አገር በፍጥነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል የተባለው ነው፡፡
በዚህ መንገድ የኢትዮጵያ ተስፋ የሚሆነውና የዚህችን አገር እድል የሚወስነው ፈጣን ልማትን ማረጋገጥ ነው፡፡ በዚህ ፈጣን ልማት ህዝቡ ተሳታፊ የሚሆንበትንና ከልማቱም ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ማመቻት የግድ ይላል፡፡ ይህ ፈጣን ልማት በአንዴ ታይቶ የሚቆም ሳይሆን በየጊዜው ከደረስንበት የእደገት ደረጃ ጋር የሚመጥን፤ እየሰፋና እየዳበረ የሚሄድ ከመሆኑም በላይ በሂደቱ የሚሳተፉትን አካላት ሁሉ ተጠቃሚና ባለቤት የሚያደርግ መሆን አለበት፡፡
በዚህም አገራችንን ከነበረችበት ድህነት፣ ኋላ ቀርነትና ጉስቁልና እያወጣን እንዲሁም ደግሞ ከዓለም አቀፍ ተመጽዋችነት እያላቀቅን ራሳችንን የቻልን በባህላችን፣ በታሪካችን እንዲሁም በህዝባችን አቅም የምንኮራ ህዝቦች አገር እንሆናለን የሚል በግልጽ የተቀመጠ ጉዳይ አለ፡፡ በዚህ ጊዜ መስመራችን ልማት ነው፡፡ ጠላታችን ደግሞ ድህነት ነው፤ የሚያደናቅፈንና ከልማት በተጻራሪ የቆመ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር በየጊዜውና በየደረጃው የስርዓታችን አደጋ ሆኖ ይቀጥላል የሚል ግምገማ ነው የተቀመጠው፡፡
ስለዚህ ከተሃድሶ ማግስት የተደረጉ ጉዳዮች አንደኛ መስመሩን መዘርዘር፣ የፈጻሚ ኃይሎችን አቅም መገንባት፣ ማሳመን፣ ማሰማራትና ወደተጨባጭ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ማስገባት ነው፡፡ ይህ የሆነው 1993 ዓ.ም ነው፡፡ በዚህም ስልት እስከ 1996 በሚባል ጊዜ የመጀመሪያውን እድገት ማስመዝገብ የጀመርነበት ወቅት ነው፡፡
ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ደግሞ የሆነው ፈጣን ልማትን ያለማቋረጥ እያስመዘገብን መምጣታችን ነው፡፡ ፈጣን ልማቱ ባደገ ቁጥር ደግሞ ዴሞክ ራሲውም በልማቱ ልክ አይሁን እንጂ እያደገ የመጣበት ሁኔታ ታይቷል፡፡ የህዝቡ የለውጥ ፍላጎትና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው የሄደው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ከዚህ ጎን ለጎን የኪራይ ሰብሳቢነት አቅሙም እየተጠናከረ ነው የሄደው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በህዝቡ የልማትና የለውጥ እንቅስቃሴዎች የተቀሰቀሱ የመሞገት ፍላጎት በአግባቡና በፍጥነት መመለስ ባለመቻላችን ምክንያት ወደ ቀውስ፣ ግጭትና አለመረጋጋት የገባንበት ሁኔታ ነበር፡፡ በ2006 ዓ.ም ሚያዝያ ወር አካባቢ በተወሰኑ የአገሪቱ አካባቢዎች፣ በኋላ ላይም በ2007 ዓ.ም የተወሰነ አካባቢም ችግሩ ነበር፡፡ ነገር ግን ምርጫ 2007 ከተጠናቀቀ በኋላ ያለማቋረጥ 2008 ዓ.ም የዜጎች ህይወት መጥፋት፣ የንብረት መውደም፣ የሰላም ማጣትና መደበኛ የስራ እቅስቃሴ መስተጓጎል የጀመረበት ሁኔታ አጋጥሞናል፡፡
ይህ ችግር ለምን ተፈጠረ በማለት መቀሌ ላይ 2007ዓ.ም ነሐሴ ወር ላይ ባካሄድነው ጉባኤ ስርዓቱን በዋናነት በጥልቀት ለማየት ተገደናል፡፡ በመሆኑም የመልካም አስተዳደር ችግር ባለመፍታታችን፣ የህዝቡንም ጥያቄ በፍጥነት ባለመመለሳችን ነው ብለን ነበር አስቀምጠን የነበረው፡፡
ህዝቡ መሞገትና መጠየቅ ሲጀምር መመለስ ያቃተንና የልቻልነው በየደረጃው ያለው ኃይላችን የመልካም አስተዳደር ችግር ስላለበት ነው፡፡ ይህን መፍታት አለብን ብለን በመቀሌ ጉባኤ ተወስኖ የነበረው በአግባቡ ባለመመለሱ ምክንያት ውስብስብ ችግር ውስጥ ገብተናልና፤ ራሳችንን መፈተሽ አለብን በሚል የ2008 ዓ.ም የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ በመደረጉ ከክረምቱ ጀምሮ ወደስራ የገባንበት ሁኔታ ነበር የነበረው፡፡
ግምገዎችን እንዳጠናቀቅን እየተከሰቱ የነበሩ ግጭቶች ሰፋፊ ስለነበሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በኋላ በአንጻራዊነት የአገሪቱ ሰላም ሰፍኖ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በተወሰነ ደረጃ መረጋገት መታየት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ እንደገና በማገርሸቱ አሁን ላይ እንደገና የአስቸኳይ ጊዜ ሊታወጅ ግድ ብሏል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከቅርብ ጊዜያት ጀምሮ ብሄራዊ ድርጅቶቹ ከአንድነት ይልቅ የእኔነት ስሜት እየተንጸባረቀባቸው በመሆኑ ለመከፋ ፈላቸው ዋና ማሳያ ሆኗል ይባላልና ምንድነው ምላሽዎ?
አቶ ሽፈራው፡- ስርዓታችን በእድገት ውስጥ ያለ ነው፡፡ በዚህ ስርዓት ውስጥ መታየት ያለበት ጉዳይ እያንዳንዱ ድርጅት አንድ ላይ ሆነን ለመታገል ስንስማማ አንድ ያደረገን ዓላማ መኖሩ ነው፡፡ ለዚህም የምንመራበትና የምንተዳደርበት ህገ ደንብ እና መመሪያ አለ፡፡
ስለዚህ ለእኔ ከባድ መስሎ የሚታየኝ ሰዎች እንዴት ነው ባህሪያቸውን እየገለጹ ያሉት የሚለው ሳይሆን ድርጅቶቻችንን ለዓላማችንና ለመርሃ ግብሮቻችን እንዴት ጸንተው ቆሙ የሚለው ነው፡፡ የህዝቦቻችን ጥቅሞቻቸውና መብቶቻቸው እንዲከበሩ እንዴት ተንቀሳቀሱ የሚለው ነው፡፡
እንዲያም ሆኖ ግን ‹‹የምትወጣው በዚህ ነው፤ የምትገባው ደግሞ በዛኛው ነው›› ተብሎ በማሽን ተቆርጦ እንደተሰራ እቃ ይሆናል ተብሎም መታሰብ የለበትም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአንዴ እንደ ደራሽ ውሃ ፈሰን ታሪክ በመቀየር የቆምንለትን ዓላማና መስመር ትተን መሄድ የለብንም፡፡ እኔ እንደሚገባኝ የቆምንለትን ወሳኙን ጉዳይ ማለት ዓላማና የዓላማው መሰረት በሚሸረሽርና በሚንድ መንገድ መሄድ በጣም መጥፎ ነው፡፡ ነገር ግን ከአዲሱ ትውልድ አዲስ አስተሳሰብ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ጉዳዮችን ለማስተካከል ግን ለውጦች መኖራቸው ነውር አይደለም፡፡
ተደራጅተን የምንታገልበት ዋና ግቡ ህዝብን ለመጥቀም ብሎም አገርን በእድገት ለመለወጥ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ማንኛውም ተገዢ መሆን አለበት፡፡ ማንም ከህዝብና ከአገር በላይ አይደለም፡፡ ለዚህ ስርዓት ነው የሚገዛው ማለት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ሲሆን፣ በኢህአዴግ ህገ ደንብ አሰራር መሰረት ተወያይተን እንፈታለን፡፡ ግለሰብ ከሆነ ደግሞ በየብሄራዊ ድርጅቱ ይታረማል፡፡ ድርጅት ከሆነ ደግሞ በኢህአዴግ መድረክ ይታረማል ማለት ነው፡፡ በዚህ መንገድ ነው ልዩነቶቻችንን የምናስተካክለው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በወጣቱም ሆነ በሌላው ኃይል እየተነሱ ላሉ ጥቄዎች በተገቢው መንገድ ምላሽ ያለመስጠት ችግሮች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል፤ እነዚህን ችግሮች ደግሞ አንዱ የአመራሩ ነው ሲል ሌላው ደግሞ የስራ አስፈጻሚው ሌሎች ደግሞ የየሊቀመናብርቱ ነው ሲሉ ይደመጣሉና እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ሽፈራው፡- ድርጅቱ ራሱን ከገመገመ በኋላ ኃላፊነትንና ተጠያቂነትን መውሰድ ያለብኝ እኔ ነኝ ብሎ ወሰዷል፡፡ እንደ ድርጅት የከፍተኛ አመራሩ ጉድለት ነው ብሎ ወስዷል፡፡ ከከፍተኛ አመራሩም የስራ አስፈጻሚው ነው ብሎ አምኗል፡፡ ይሁንና እያንዳንዱ ግለሰብ ግን የራሱ የሆነ ድርሻ አለው፡፡ ድርሻው ደግሞ ስኬትም ጉድለትም ሊሆን ይችላል፡፡ አንዱ ላይ ብቻ የምንጠቁምበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ እያንዳንዳችን ለመስመሩ የቆምን ሁሉ እኩል ባልደረቦች ነን፡፡ ልዩነታችን ስምሪት ብቻ ነው፤ እንደየስምሪታችን ልክ ደግሞ ኃላፊነትም ተጠያቂነትም አለብን፡፡ ስለዚህ ጥፋቱ የእከሌ አሊያም የእከሊት ነው ተብሎ የሚባል አይደለም፤ የሁላችንም ነውና፡፡ ግን ደግሞ በዋናነት የከፍተኛ አመራሩ ሲሆን፣ ከከፍተኛ አመራሩም ደግሞ የስራ አስፈጻሚው ነው፡፡ ስለዚህም በየነበረበት ራሱን እንዲፈትሽ ነው የተባለው፡፡ ችግሩ ከግንባሩ ሊቀመንበር ጋር ብቻ የሚጣበቅ አይደለም፡፡
አንዳንዴ ደግሞ መረዳት ያለብን ጉዳይ ተፈጠሩ የተባሉትን ችግሮች አንዳንዶቹን የቱንም ያህል ብንሰራ ልንፈታቸው የማንችላቸው ናቸው፡፡ የህብረተሰብ እድገት ለሚያመጧቸው ጥያቄዎች መፍትሄ እናመጣለን እንጂ፤ ችግር የሌለበትን ህብረተሰብ እንገነባለን አላልንም፡፡ ወደፊትም እንደዚህ ብለን ካሰብን ቅዠት ነው የሚሆንብን፡፡ ችግሮች ወደ ቀውስ እንዳይሻገሩ እናደርጋለን እንጂ ሙሉ ለሙሉ ፈተን እንጨርሳለን ማለት አይደለም፡፡ በፈታን ቁጥር አዲስ ፍላጎት ይቀሰቀሳል፤ አንዱን እንፈታለን፤ እንዲሁ አዲስ ፍላጎት ይቀሰቀሳል፡፡ ይህ የማያቆም የህብረተሰብ የእድገት ለውጥ ነው፡፡
እንዲያም ሆኖ ወደ እውነታው ስንመጣ አሁን ችግሮች አሉብን፤ በውስጣችን የስልጣን እይታ ብልሽትና የፓርቲ መበስበስም ስላጋጠመን ነው ወደ ችግር የገባነው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ይህንን ማስተባበል የሚቻልበት እድል ያለ አይመስለኝምና ለችግሮቹ መፍትሄ ማምጣት የአመራር ኃላፊነት ስለሆነ በዚህ መንገድ ማየቱ መልካም ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢህአዴግ ግንባር መሆኑ ነው መከፋፈሉን የሚፈጥርበት የሚሉ አካላት አሉና ውህድ ፓርቲ የመሆኑ ጉዳይ ከምን ደረሰ?
አቶ ሽፈራው፡- ውህድ ያልሽውን ለጊዜው እናቆየውና ኢህአዴግ አንድ አገር አቀፍ ፓርቲ መሆን አለበት የሚለው መወሰን አለበት፡፡ የችግራችን ምንጭ አንድ ያለመሆናችን አይደለም፡፡ እኛ ስልጣን ለመከፋፈል የተደራጀን ኃይል አይደለንም፡፡ በአንድ መርሃ ግብር ዙሪያ በተለየያ አካባቢ የተደራጀን ኃይሎች ነን፡፡ የተለያየ መርሃ ግብር የለንም፤ በሶስት ቋንቋ የተጻፈ አንድ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መርሃ ግብር ነው ያለን፡፡ ስለዚህ በመሰረታዊነት አንድ ስንሆን የሚለየን የቅርጽ ጉዳይ ነው ማለት ነው፡፡
ነገር ግን ብሄራዊ አደረጃጀታችን በዘላቂነት አንድ አገራዊ ፓርቲ ለመሆን ከግንባርነት ወጥተን መሄድ ያስፈልገናል፡፡ የአሁኑ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ከዚህ በፊት በጉዳዩ ጥናት ይጠና ሲባል የነበረውን ጉዳይ ተነጋግሮ ማስተካከል አለበት የሚል ውሳኔ ወስኗል፡፡ በዚህ መሰረትም በአሁኑ የነሐሴ ጉባኤ አንድ የውሳኔ ሐሳብ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኢህአዴግን ውህድ ማድረግ ብቻም ሳይሆን አጋር ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት እንዲሁ የሚታይ ነው የሚሆነው፡፡ እስካሁን ድረስ አጋር ሲባሉ ቆይተዋል፡፡ ከዚህስ በኋላ አጋር እየተባሉ ይቆያሉ ወይስ አይቆዩም የሚለውም ጉዳይ አንድ የውሳኔ ሐሳብ ቀርቦ መቋጫ የሚያገኝ ነው የሚሆነው፡፡ ኢህአዴግም ግንባር ሆኖ ይቆያል አይቆይም በሚለውም ጉዳይ ላይ እንዲሁ፡፡
ይህ የውሳኔ ሐሳብ እንዴት ሊደራጅ ይችላል በሚለው ዙሪያ ቀጣይ መፍትሄንም የሚያቀርብ ይሆናል እንጂ የነሐሴው ጉባኤ ላይ አንድ አገራዊ ፓርቲ ላይመሰርት ይችላል፡፡ ነገር ግን እስከሚቀ ጥለው ጉባኤ አሊያም መሃል ላይ አገራዊ ፓርቲ እንዴት እንመስርት በሚለው ጉዳይ ላይ የመፍትሄ ሐሳብ ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡
ይህ በራሱ ግን ችግር አይደለም፡፡ ችግሩ በመርሃ ግብሩ ዙሪያ ያለው የዓለማ ጽናት እና የሕዝብ ወገንተኝነት መሸርሸር ካለ አንድ ፓርቲም ይፈርሳል፡፡ አሁን ባለንበት መርሃ ግብርም በጽናት እና በታማኝነት ለመስመራችን ኪራይ ሰብሳቢነት ሳይፈትነን ከቀጠልን ለውጡን ልናመጣ እንችላለን፡፡ ነገር ግን ቢያንስ ላለፉት 26 ዓመት ገዥ ፓርቲ ሆነን ቆይተናል፡፡ በእነዚህ ጊዜያትም በስምምነት በዓላማ ጽናት በመሄድ በርካታ ችግሮችንም የፈታንባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡
በቀጣይ የምናካሄደውም ጉባኤ ልክ እንደቀ ድሞው ሁሉ በጥልቀት ራሱን በማየት ችግሮችን እንዲፈታ ከነበረው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በተጨማሪ ሌላ ተደራጅቶ ድርጅትን እንደገና የማጠናከር ስራ ይሰራል፡፡ ችግሩን ለመፍታት የሚደራጀው አካል ተግባር ግልጽ አሰራር ማበጀት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የጸደ ቀበት ሒደት ‹‹የተጭበረበረ ነው›› የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ሁለት ሶስተኛ መሆን ያለበት ከጠቅላላው ከ547ቱ አባላት ነበር የሚሉም አካላት አልታጡምና እርስዎ እዚህ ላይ አስተያየትዎ ምንድነው?
አቶ ሽፈራው፡- እኔ አሁን ላነሳሽው ጥያቄ የምናገረው እንደ ምክር ቤት አባል ሆኜ ነው፡፡ የፓርቲው አቋምም ቢሆን ግልጽ ነው፡፡ ስርዓታችን ፓርላሜንታዊ ነው፡፡ ሰርዓታችን እያንዳንዱ ፓርቲ፣ የፓርላማ አባል ፓርቲውን ወክሎ የፓርላማ አባል ሆኖ ሲመረጥ የትም ዓለም የትኛውንም አይነት ስርዓት የሚከተል ቢሆን ፓርላሜንታዊ እስከሆነ ድረስ የፓርላማ አባል መጀመሪያ በአንድ አጀንዳ ላይ የአፈጻጸም ከሆነ መብቱ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሪፖርት በሚቀርብበት ጊዜ ገምግሞ ልክ ነው ልክ አይደለም በማለት የተለያየ አቋም መያዝ ይችላል፡፡
ነገር ግን ፖሊሲ ከሆነና የፓርቲው አቋም ከሆነ ግን በፓርቲ መድረክ ወደ ፓርላማው ከመግባቱ በፊት ባለው መድረክ ላይ ክርክር ያካሂዳል፡፡ በዛ መድረክ እስከመጨረሻው ድረስ ተከራክሮ ይተማመናል፡፡ በመጨረሻ ግን ፓርቲው አቋም ከወሰደ የፓርቲውን አቋም ይወስዳል እንጂ የተለየ አቋም አይዝም፡፡
ይህን ለማድረግ በምክር ቤት የፓርላማው ስብሰባ ከመጀሩ አስቀደሞ የፓርቲ መድረክ ላይ የኢህአዴግ የአራቱም ድርጅቶች ሊቀመናብርት ተገኝተናል፡፡ እንዲሁም አምስቱም የአጋር ድርጅቶች ተገኝተዋል፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊትም እያንዳንዱ የኢህአዴግ አራቱ አህት ድርጅቶች ለየብቻቸው ከየአባሎቻቸው ጋር መክረዋል፡፡
በመሆኑም የኢህአዴግ አራቱም ሊቀመናብርት በጉዳዩ ላይ አስተያየት ሰጥተንና ተስማምተን፤ አዋጁ በተባበረ ድምጽ እንደሚጸድቅ ወስነን ነው የተለያየነው፡፡ ይህ የአዋጁ መጽደቅ እንደየፓርቲያችን የአራታችንም አቋም ሲሆን፣ እንደግንባራችንም የስራ አስፈጻሚ ውሳኔና አቋም ነው፡፡ አራታችንም በጋራ ነው የወሰነው፡፡ ይህን ያደረግነው ደግሞ በዋዜማው የፓርላማ አባላት ሁሉ ባሉበት ሐሙስ እለት ነው፡፡
አዋጁ ከመጽደቁ አስቀድሞ ገና በመጀመሪያው ላይ አፈ ጉባኤው የተናሩትን ማስታወስ ካስፈለገ ከ547ቱ የምክር ቤት መካከል አራት ሰዎች በህይወት የሉም፤ አራቱ ደግሞ በተለያየ ምክንያት በአገር የሌሉ ናቸው፡፡ ቀሪ የሚሆነው 539 ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 490 ሰው በዚህ ምክር ቤት ውስጥ አለና ምላዕተ ጉባኤው ተረጋግጧል ብለው ነው ስብሰባውን ያስጀመሩት፡፡ ይህንን በእለቱ ያሉት የመገናኛ ብዙኃን ሰምተዋል፡፡
ከዛ ውይይቱ ከተካሄደ በኋላ አባላቱ በተባበረ ድምጽ ሳይሆን ድምጽ እንሰጣለን ባሉት መሰረት ነው ድምጽ የተቆጠረው፡፡ ሲቆጠር ቆጣሪዎቹ የፈጠሩት ስህተት አለ፡፡ በመሆኑም ለአፈ ጉባኤው ሲቀርብ የሆነው 88 ተቃውሞ፣ ሰባት ድምጸ ተዓቅቦ መሆኑን ሁሉም የሰማው ጉዳይ ነው፡፡ ከ490 ላይ የተጠቀሱት ቁጥሮች ሲቀነሱ የሚቀረው 395 ነው፡፡ ይህ ቁጥር ደግሞ ለ539 ሲካፈል 70 በመቶ ነው የሚሆነው፡፡ ሲቀንሱ ግን አፈ ጉባኤው የተናገሩት 346 ነው፡፡ ይህ ቁጥር ግን ለ490 አይደለም የተካፈለው፡፡ ከህግ አንጻር የሚያከራክር ጉዳይ አለ፡፡ አሁን ወደእዛ መግባቱ አስፈላጊ አልመሰለኝም፡፡ ይሁንና የተካፈለው ላልመጣውም ለ539 ነው፡፡ በእለቱ ለምሳሌ 49 ሰው አልመጣም፡፡ ይህ ድምጽ እንግዲህ ለሌሉትም ጭምር ነው የተካፈለው፤ እንዲያም ሆኖ 70 በመቶ ነው የሚያሳየው፡፡ ለ490 ቢካፈል ደግሞ 80 በመቶ ያህል ነው የደገፈውና በሁለቱም ቢሰላ ለአዋጁ መጽደቅ ለውጥ የለውም፡፡
ሌላው ደግሞ የእያንዳንዱ ብሄራዊ ድርጅት ሆነ የአጋር ደርጅት ማን ድምጽ እንደሰጠ በግልጽ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህም በካሜራ የተቀረጸ ጉዳይ በመሆኑ ካስፈለገ ተመልሶ ማረጋገጥ የሚቻል ነው፡፡ መጀመሪያውኑ ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዳይጸድቅ የፈለጉ አካላት የህዝቡ ሰላምና ደህንነት እንዳይረጋገጥ የሚፈለጉ ናቸውና የፈለገውን ያህል ጽድቅ ብንሰራም ለእነሱ ኩነኔ መሆኑ አይቀርም፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዋና ዓላማ ‹‹ይጠቅ መናል›› ብሎ መንግስትና ድርጅት አምኖ በስራ አስፈጻሚ ደረጃ ሁለት ዙር ተወያይቶ የወሰነው ውሳኔ ነው፡፡ በዚህም ስምምነት ላይ መድረስ ችሏል፡፡ በመሆኑም በእኔ እምነት በፓርቲዎቹ መካከል ችግር አለ ብዬ አላምንም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የ88ቱ አባላትን መቃወም አንዳንዱ የዴሞክራሲ መገለጫ ነው ሲለው ሌላው ደግሞ ከዚህ ቀደም እንዳጋጠመው አይነት የመስመር ዝንፈት ነው ይላሉ፤ በዚህስ ላይ ምን አስተያየት አልዎት?
አቶ ሽፈራው፡- አንድ መታሰብ ያለበት ነገር በታሀድሶ ጊዜ የነበረውና የአሁኑ የተለየ መሆኑ ነው፡፡ የመስመር ልዩነት ሲኖር ከጅምሩ አግባብነት ያለው ክርክርና ውይይት ኖሮ፣ የመስመር ልዩነት መኖሩን አስታውቆ፣ በልዩነቱ ላይ ድምጽ ሰጥቶ ተሸንፎ ወይ አሸንፎ፣ የራስ ሐሳብ የበላይነት ስላላገኘ ከማዕከላዊ ኮሚቴ፣ ከምክር ቤት ወደ ካድሬው ሄዶ በመሸነፍ የወጣ ነው፡፡ ውህዳኑ የብዙሃኑን ውሳኔ ባለመቀበላቸው መብታቸው ተጠብቆላቸው ነው የሄዱትና ይህ ሌላ ታሪክ ነው፡፡
የአሁኑን በተመለከተ በታህሳሱ ስብሰባችን በድርጅቶች መካከል መጠራጠር እንደነበር ነው የሚታወቀው፡፡ ይህ መጠራጠር በከፍተኛ አመራሩ እንዲሁም ከስራ አስፈጻሚው ጀምሮ ታች ድረስ ተፈጥሮ እንደነበርና ይህን ችግር መፍታት እንዳለብን ተስማምተናል፡፡ በዚህ ጉዳይ አንዳንድ ድርጅቶች እስከ ካድሬ ድረስ ሄደው ችግሮችን በመፍታት፣ የሌሎች ድርጅቶች ካድሬዎችንም ጠርተው የራሳቸውንም ችግር ከሌሎች እህት ድርጅቶች ጋር ያላቸውንም ግንኙነት በግልጽ ውይይት አድርገው ባቸዋል፡፡
በአንዳንዶቻችን ድርጅቶች ደግሞ ገና ስራ አልተሰራም፡፡ ስለዚህ የቤት ማጽዳት ስራው ገና አላለቀም ማለት ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ እያለን ነው የሰላም እጦት በማጋጠሙ ወደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሄድ ላይ ሳለን ይህ ያጋጠመን፡፡ በእኔ እምነት ግን ጠቃሚ የሚመስለኝ በተከሰቱ ጉዳዮች ላይ ቀጣይ ውይይት በማካሄድ በድርጅታችን የመስመር ልዩነት ነው ወይስ የክስተት ነው የሚለው ላይ በደንብ መነጋገር አለብን፡፡
የተፈጸመው ስህተት ነው፡፡ ነገር ግን በአንድ ስህተት እንደዚህ አይነት የመስመርና የድርጅት የመለያየት ጉዳይ አድርገን ባንወስደው መልካም ነው፡፡ ችግሮቹ በዝርዝር ቢፈተሹና ምንጫቸው ቢታይ እንዲሁም ያልተግባባንባቸው ጉዳዮች ቢጠሩ ነው ወሳኝ የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ የሚበልጡ ሌሎች ዋና አጀንዳዎች አሉና ይህን እየፈታንና በሂደትም የተፈጠርን ችግር በነበረው የመተራረም ባህላችን እናርመዋለን በዬ አስባለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የግንባሩ ሊቀመንበር ከሊቀመንበርነቱ ከተሰናበቱ በኋላ እጣ ፈንታቸው ምንድነው?
አቶ ሽፈራው፡- የተለየ አዲስ ነገር አይኖርም፡፡ እንደ አንድ የኢህአዴግ ታጋይ በትግሉ ይቀጥላሉ፡፡ ስምሪታቸው ግን በአገሪቱ ህገ መንግስት መሰረት የስራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁ ጠቅላይ ሚኒስትር በሚተዳደሩት መንገድ ይተዳደራሉ፡፡ ይህን የተመለከተ ህግ አለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለቃለ ምልልሱ ስለተባበሩኝ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ሽፈራው፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አስቴር ኤልያስ

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።