Items filtered by date: Tuesday, 13 March 2018

በጥቁሮች ታሪክ ዝክር ያሳለፍነው ወርሃ የካቲት፣ መላው የጥቁር ሕዝብ በባርነት ቀንበር ሲማቅቅና ነጭ ገዥዎች በአማልክት ደረጃ ሲከበሩ በነበረበት በዚያ ዘመን፣ የጨለመው ጥቁር ሰማይ ላይ የነፃነት ፀሐይ የፈነጠቁ እንዲሁም የማንነት ሚዛን አመጣጥነው የኃያልነት ትርጓሜ የቀየሩ ውድ ጥቁሮች ተጋድሏቸው፣ ሕይወታቸውና ስኬቶቻቸው ይዘከራል።
በምክንያትና በአመክንዮ ስለ ሰብዓዊነት፣ እኩልነትና ነፃነት የታገሉና በዘመኑ በቸልታ ጥላ ተሸፍነው የነበሩ ጥቁሮች አደባባይ ይወጣሉ። በነፃነት ተጋድሎ ለእኩልነት መስረጽ የልዩነት ተረኮችን ለማስቀረት በሁሉም ዘርፍ ማለትም በፖለቲካ፣ በማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸው ታሪክ የሰሩ ጥቁሮች ይደምቃሉ። ላመቻቹት ከፍታና ለአበርከቷቸው ሥራቸውና ስማቸው ይዘከራል፤ ይታወሳልም።
ምስጋና የጥቁሮች ታሪክ ዝክር አባት የተባሉት ዶክተር ጥቁር አሜሪካዊው ካርታር ውድሰን ይግባና እአአ 1926 የጥቁሮች ወር እንዲታሰብ ሃሳብ ካቀረቡ ጀምሮ በርካታ ጥቁር ኮከቦች በአደባባይ ይዘከራሉ። ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የትናንትን ታሪክ ለዛሬ ጥቁር ሕዝቦች ኩራት ለሆኑ ጥቁሮች የአፀፋ ውለታ ምላሽ ፍቅር፣ ምስጋና፣ አድናቆት እንዲሁም ሰላምታ ይዥጎደጎድላቸዋል። መዛግብታቸው ይገለጣል። በልፋትና ድካማቸው የዘሩትን ያጭዳሉ። የበተኑትን ይሰበስባሉ። ለድካማቸውም እውቅና ያገኛሉ። የተጋድሏቸውን ታሪክ ጀርባ ማንነቱንም ሆነ ምንነቱ በብዙ ተገልጦ ብዙዎች ይመለከቱታል፤ ያውቁታልም።
በጥቁሮች ወር ትናንት የእምቢታ ድፍረት በፈፀሙት ተግባር የዛሬ ስኬት የሆኑ ጥቁሮች የማንነት ከፍታቸውና የመንፈስ ልዕልናቸው ያይላል። በየቦታውና በየዘመኑ ድንበር ያልገደባቸው፣ ዘር ሐረግ ያልሳባቸው፣ ቀዬና ቋንቋ ያልጠራቸው፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ ሆነ ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ለውጥ ያመጡ ማርቲን ሉተር፣ ኔልሰን ማንዴላንና የመሳሰሉ ምርጥ ጥቁሮች ይታወሳሉ።
ባሳለፍነው ወር በተለይ በስፖርቱ ዘርፍ በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች በዘርና በቆዳ ቀለማቸው ይደርስባቸው የነበረውን አጥር ጥሰው በየትኛውም መድረክ ተፎካካሪ ብሎም አሸናፊ መሆን የቻሉ የጥቁሮች ኮከባቸው ይበልጡኑ ያንፀባርቃል። «ሥልጡን ነኝ» ባዩን ነጭ በእምነት፣ በአንድነትና በቆራጥነት አሳምኖ ለማሸነፍ ጠብመንጃ ያላስፈለጋቸው ለጥቁር ነፃነት ደም ሳይሆን ላብ የገበሩ ጥቁሮች ይታሰባሉ።
በስፖርቱ ዓለም ዘረኝነትን የታገሉ፤ እኩልነትን ያንፀባረቁና በድላቸው የጥቁር ሕዝቦችን አንገት ያቀኑ እና ትርጉም ያለው ድል በርካታ ጥቁር ከዋክብት በዚህ ባሳለፍነው የካቲት ወር ሳይዘከሩ አይታለፉም። ከእነዚህ ድላቸው ትርጉም ከነበረው ጥቁር ስፖርተኞች መካከል ጥቂት ጥቁር አሜሪካውያንን እንመልከት።
አገሩ ሜክሲኮ፣ ወቅቱና ሁነቱ ደግሞ እአአ 1968 የተካሄደው ኦሎምፒክ ነው። የታሪኩ ባለቤቶች ደግሞ አሜሪካ የአጭር ርቀት ተወዳዳሪዎች ጆን ካርሎስና ቶሚ ስሚዝ ናቸው። እነዚህ ጥቁር አሜሪካውያን በዚህ ኦሎምፒክ በተወዳደሩበት ርቀት የወርቅ እና የብር ሜዳሊያ አጥልቀዋል። ማሸነፋቸው ብቻውን ግን ለእነርሱም በቂ አልነበረም። ድላቸው ትርጉም ነበረው። መላው የጥቁር ሕዝብ ከባርነት ቀንበር እንዲላቀቅ ሁነኛ መልዕክትን ያስተላለፈ ነው። የጨለመው የጥቁር ሰማይ ላይ የነፃነት ፀሐይ እንዲፈነጥቅ ምክንያት ሆኗል።
የማንነት ሚዛን ተመጣጥኖ እንዲታይ ያደረገው የሁለቱ አትሌቶች ተግባር በሽልማት ሰገነቱ ላይ የተተወነ ሲሆን፣ በወቅቱ አንደኛው ቀኝ፤ ሌላኛው ደግሞ ግራ እጁን ከፍ በማድረግ የጥቁር አሸናፊነትና አንድነት ምልከት ተገልጾበታል፡፡ ጥቁር ካልሲ ብቻ በማድረግ ጫማ ሳይጫሙ ሰገነቱ ላይ የመቆማቸው ምልክት ደግሞ የጥቁሮችን ድህነት እንዲያሳይ ታሳቢ ያደረጉት ነው።
በዚህ ተግባራቸው በቆዳ ቀለም የሚመስላቸው በሃሴት ፊታቸው ሲበራ፣ በቆዳ ቀለም የማይመስ ሏቸውና ዘረኞቹ በአንፃሩ ፊታቸው ጠቁሯል። የንዴታቸው ጥግ ማሳያ ደግሞ አትሌቶቹ ከስፖርታዊ ውድድር እንዲታገዱ ማስደረጋቸው ነው። ማናቸውም ግን በተግባራቸውና በውጤቱ ቅንጣት ያህል አልተፀፀቱም።
ዘረኛ ነጮችን አንገት ካስደፉና የጭቁን ጥቁሮችን እንባ ደግሞ በሳቅ ከቀየሩ ስፖርተኞች አንዱ ደግሞ ጥቁሩ አሜሪካዊ አትሌት ጄሴ ኦውንስ ነው። የአትሌቱ ገድል መቼቱን ያደረገው ደግሞ የ1936ቱን የበርሊን ኦሊምፒክን ነው።
በዚህ ኦሎምፒክ ዘረኛው የናዚ መሪ አዶልፍ ሂትለር አይሁዶችንና ጥቁሮችን የበታች ሆነው እንዲታዩ ባቀደውና በቀመረው ስሌት መሠረት ሁሉንም አሰናድቶ ነበር። ጄሴ ኦውንስ ግን ይህን ጥረት ውድቅ አድርጎ አምባገነኑን መሪ ሎች ዝርኛ ጋሻጃግሬዎቹን በአደባባይ አንገት ያስደፋ ታሪክ ሰርቶበታል።
አትሌቱ፣ በመድረኩ ሁለት የዓለም ክብረ ወሰንና አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን የግሉ ማድረግ የቻለ ሲሆን፣ ስፖርት የቆዳ ቀለም ሳይሆን የችሎታ ልዩነት ውጤት መሆኑንና ጥቁሮች ዕድል ካገኙ ስኬታማ የማይሆኑበት ምክንያት እንደሌለ አስመስክሯል። ይህ አልዋጥለት ያለውና ወትሮም ቢሆን በአሜሪካ ስፖርት ልዑካን ስብስብ ውስጥ የጥቁር ስፖርተኞች ስም መካተቱ ያንገበገበው ሂትለር ግን፣ በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ኦውንስን የ«እንኳን ደስ አለህ» ሰላምታ ነፍጎታል። ላለመጨበጥና ለድሉም እውቅና ላለመስጠትም ስታዲየሙን ለቆ ለመውጣት ተገዷል።
ይህን ድል አለማድነቅ ክፋት ካልሆነ ሊሆን የሚችለው አለመታደል ብቻ ነው። ይሁንና ከሂትለር በተጓዳኝ በየወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ሩዝቬልትም ተመሳሳይ ተግባር ፈፅመውበታል። ከኦሎምፒክ ስኬቱ መልስ አገሩ ሲደርስ የጀግና አቀባበል አልተደረገለትም። አገሩም ቀይ ምንጣፍ ዘርግታ «ጀግናዬ» አላላቸው፤ አሊያም ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት አልተጋበዘም። እርሱም ቢሆን ከአምባገነኑ ዘረኛ መሪ ሂትለር ባሻገር የአገሩ ፕሬዚዳንት እንዳሳፈሩት ተናግሯል።
ይህ ገድሉ በዘረኛ ነጮች እውቅና ይነፈገው እንጂ ነጮች ወደዱም ጠሉም ከጥቁሮች እኩል እንደሆኑ ልቦናቸው እንዲያምን አስገድዷቸዋል። ድሉም በተለይ የነጭና የጥቁር ውድድሮች በሚል ተከፍሎ ይካሄድባት በነበረችው አሜሪካ ትልቅ ትርጉም ነበረው። አትሌቱ በአገሩም ሆነ ከአገሩ ውጪ የሰራው ይህ ታሪክም ሁሌም ስለ ጥቁሮች ብልጫነት ሲወሳ ስሙ አብሮ እንዲነሳ ምክንያት ሆኖ ይታወሳል።
እአአ 1908 ነጩን ቡጢኛ ጂም ጄፈርስንን በቦክሱ ክልል ከአስራ አምስት ዙር ፍልሚያ በኋላ ጉድ የሰራውና የመጀመሪያው አፍሪካ አሜሪካዊ ጥቁር የከባድ ሚዛን ሻምፒዮና ጃክ ጆንስን ቀጥሎ ስሙ የሚገነው ደግሞ የምንጊዜም የቦክስ ስፖርት ንጉሡ መሐመድ አሊ ነው። አሊ ለሁለት አስርት ዓመታት በዘለቀ በቦክሱ ክልል ከአይበገሬነቱ ባሻገር ከሜዳ ውጪም ብዙ ነጭ ዘረኞችን ዘርሯል። ከሜዳ ላይ ብቃት አነጋጋሪነቱ በላይ ከሜዳ ውጪም የዘር መድልዎን በመቃወም ለብዙዎች አነጋጋሪ ሆኗል። ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ በቆዳ ቀለም ከሚመስሉትና ከተጨቆኑ ወንድምና እህቶቹ ጎን በመቆም ይታወቃል። ድምፁን ከፍ አድርጎ በደላቸውን አስተጋብቷል።
አሜሪካ በቬትነሃም ላይ የከፈተችውን ጦርነት አግባብ አለመሆኑን በይፋ ተቃውሞ፤ ለዘመቻ ከመሄድ ራሱን አቅቧል። ጦርነቱን በመተቸቱና ከጭቁኖች ጎን በመሰለፉም የኋላ ኋላ ቢመለስ ለትም የቦክስ ፍቃዱን እስከመነጠቅ አድርሶታል። የቦክሱ ንጉሥ፣ ይህ ተግባር እያደር የሚረዳው አግኝቶ ዛሬ በርካታ ጥቁሮች አንገታቸውን ቀና አድርገው ለመሄዳቸው ወሳኝ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በ1970 የዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ መታሰቢያ ሽልማት የተቀበለው መሐመድ አሊ፤ የዓለም አቀፋዊ ወዳጅነት ተምሳሌት ሆኗል። የተባበሩት መንግሥታት የሰላም መልዕክተኛ በመሆንም እአአ ከ1998 እስከ 2008 በታዳጊ አገራት በመዘዋወር አገልግሏል።
በጥቁሮች የነፃነት ተጋድሎ የእኩልነት መስረጽ የልዩነት ተረኮችን በማስቀረት ገድል ስሙ አብሮ ይነሳል - አርተር አሽ። ይህ ጀግናም አሜሪካዊውን ነጭ የቴኒስ ኮከብ ጂሚ ኮነርስን በማሸነፍ እአአ 1975 የዊምብልደን ሻምፒዮን መሆን ችሏል።
ጥቁሮች በየትኛውም መድረክ ተፎካካሪ ብሎም አሸናፊ መሆን እንደሚችሉ ለማሳያነት ረግቶ እንደሚሰራ በተደጋጋሚ ሲናገር የሚደመጠውና አፓርታይድን በመቃወሙ የሚታወቀው አሽ፤ እአአ 1963 በዴቪስ ካፕ አሜሪካን በመወከል የመጀመሪያው ጥቁር ተጫዋች መሆን ችሏል። ጥቁር አሜሪካዊ ሆኖ የዓለማችን ቁጥር አንድ ስፖርተኛ ደረጃን ሲይዝም እርሱ የመጀመሪያው ነው። ከሜዳ ውጪ ለበርካታ ጥቁሮች አሸናፊነት ምክንያት የሆነው ይህ ጥቁር ኮከብ፤ የአፍሪካ አሜሪካውያን አትሌቲክስ ማህበር በመመስረት ዛሬ ላይ ታይስንጌ የመሳሰሉ ጥቁር አሜሪካዊ አትሌቶች ለመታየታቸው ዋነኛውን ድርሻ ይወስዳል።
የ36 ዓመቷ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የቴኒስ ተጫዋች ሴሪና ዊሊያምስ፣ የጥቁሮች ጭቆናን በሜዳና ከሜዳ ውጪ ከተፋለሙ ኮከቦች አንዷ ናት። በሜዳና ከሜዳ ውጪ የዘረኞች ሰለባ ሆናለች። እነዚህ ሁሉ ተጽዕኖዎች ግን ከስኬታማነቷ አላገዷትም።
በዘርና በቆዳ ቀለሟ እንዲሁም እንስትነቷ ተዳምሮ ይደርስባት የነበረውን አጥር ጥሳው በየትኛውም መድረክ ተፎካካሪ ብሎም አሸናፊ መሆን እንደምትችል አሳይታለች። በቴኒስ ሜዳው ክልል የነጮች የበላይነትን ነጥቃለች። በነጮች የተያዘውን መድረክ ጥሳ በመግባት ጥቁርነትን አጉልታለች። የነጭ ተጫዋቾችና አመራሮችን የበላይነት አስወግዳለች፤ አሳክ ታለችም፡፡
ለ23 ጊዜያት የግራንስላም ሻምፒዮን ሆናለች። የዛሬን አያድርገውና የዓለማችን ቁጥር አንድ የቴኒስ ተጫዋች ስም ዝርዝር የሚጀምረው ከእርሷ ነበር፡፡ በሴቶችና በጥቁሮች ላይ የሚፈፀም አድሎ እንዲቆም አድርጋለች።
የጥቁሮች ታሪክ ዝክር አባት የተባሉት ካርታር ውድስን በዚህ ሁሉ ሊመሰገኑ የተገባቸው ነው፡፡ የባርነት ዘመን ጥቁር ጠባሳ ሽረው የጨለመው የጥቁር ሰማይ ላይ የነፃነት ፀሐይ የፈነጠቁ፣ የማንነት ሚዛን አመጣጥነው ወደ ኃያልነት ትርጓሜ የቀየሩ የውድ ጥቁሮች ተጋድሎ፣ ሕይወታቸውና ስኬቶቻቸው ነገም ይዘክርላቸዋል። ለጥቁር ነፃነት ደም ሳይሆን ላብ የገበሩ ጥቁሮች ትርጉም በሰጠውና በሚሰጠው ልፋታቸውም ዓለም ያመሰግናቸዋል፤ ያከብ ራቸዋልም።

ታምራት ተስፋዬ

Published in ስፖርት

በ ሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በዓለማችን የተለያዩ ከተሞች በርካታ የጎዳና ላይ ውድድሮች በየደረጃው ተካሂደዋል። በርካቶቹ ውድድሮች ዓለምአቀፉን የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ የተካሄዱ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል። በዋናነት በሳምንቱ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው የጃፓን ናጎያ የሴቶች የማራቶን ውድድር ሲሆን፣ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት መስከረም አሰፋ አሸንፋበታለች።
በዓለምአቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው ይህ ውድድር ከትናንት በስቲያ ሲካሄድ ከሃያ ሦስት ሺ ሰባት መቶ ሴቶች በላይ ተካፋይ ሆነዋል። በውድድሩ ኬንያዊቷ አትሌት ቫሌሪ ጄሚሊ እስከ ሰላሳ ስምንተኛው ኪሎ ሜትር ድረስ መምራት ብትችልም በስተመጨረሻ መስከረም አሰፋ በአስደናቂ ብቃት ከኋላ መጥታ ማሸነፍ ችላለች። ሴቶችን በስፋትና በብቸኝነት በማሳተፍ በዓለም ትልቁ በሆነው የውድድር መድረክ መስከረም ለአሸናፊነት የበቃችበት ሰዓት 2:21:45 ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ በውድድሩ ታሪክ ሦስተኛው ፈጣን ሰዓት መሆን ችሏል።
መስከረም ከውድድሩ በኋላ በሰጠችው አስተያየት ውድድሩ የሴቶች ብቻ በመሆኑ ለማሸነፍ ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበራት አስረድታለች። ኬንያዊቷ ጄሚሊ 2:22:48 በመግባት ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ፤ ጃፓናዊቷ ሃናሚ ሴኪን በ2:23:07 ሰዓት ሦስተኛ ሆና ፈፅማለች። አትሌት መስከረም አሰፋ እ.ኤ.አ በ2012 የለንደን ኦሊምፒክ በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ኢትዮጵያን መወከል እንደቻለች ይታወሳል።
አዲስ አበባ ላይ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ያዘጋጀው 15ኛው ቅድሚያ ለሴቶች የአምስት ኪሎ ሜትር የሴቶች የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድርም በሳምንቱ ተጠባቂ ነበር። «ከጥቃት ነጻ ህይወት መብቴ ነው» በሚል መሪ ቃል በተካሄደው በዚህ ውድድር አሥራ ሁለት ሺ ሴቶች ተሳትፈውበታል፡፡ ውድድሩ በየዓመቱ ሲካሄድ የኢትዮጵያውያን ሴቶች ስኬት ለማክበርና እውቅና ለመስጠት እንዲሁም ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ታሳቢ በማድረግ ነው። ውድድሩ በየዓመቱ መካሄዱ ሴቶችን ከመደገፍ አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አትሌት መሰረት ደፋር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ «ውድድሩ ሴቶች በማህበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ሚናና ተምሳሌትነታቸውን በማስተዋወቅ ረገድ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል» ብሏል። ሴቶች ለአገር ዕድገትና ልማት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ የገለፀው ኃይሌ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ስትሳተፍ ከወንዶቹ በተሻለ ብዙ ሜዳሊያ የሚያገኙት ሴት አትሌቶች መሆናቸውን በምሳሌነት አንስቷል።ይህም ሴቶችን ማብቃት ከተቻለ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ማሳያ እንደሆነ ተናግሯል።
በውድድሩ አትሌት ፀሐይ ገመቹ አንደኛ፣ አትሌት ደባሽ ኪላል ከሱር ኮንስትራክሽን ሁለተኛ እንዲሁም አትሌት የኔነሽ ጥላሁን ደግሞ በሦስተኛነት አጠናቃለች። ከ1ኛ እስከ 3ኛ ለወጡ አትሌቶች የዋንጫና የገንዘብ ሽልማ መበርከቱም ይታወቃል፡፡
በካታሎኒያዋ መዲና በተካሄደው የባርሴሎና ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታ ድል ባይቀናቸውም የርቀቱ ፈርጦች የሆኑት ኬንያውያን የምን ጊዜም ተቀናቃኝ እንደሆኑ ማሳየት ችለዋል። በወንዶች ኬንያውያኑ አንቶኒ ማሪቲም 2:08:08 ሰዓት፣ ሲላስ ቶ 2:08:26 ሰዓት፣ ሂላሪ ኪፕሳምቡ 2:08:53 ሰዓት ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል። በሌሎች የማራቶን ውድድሮች ትልቅ ስም ያላቸው ኢትዮጵያውያኑ ታሪኩ ጁፋርና ፀጋዬ ከበደ እንዲሁም ፀዳት አያና ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘው አጠናቀዋል። በሴቶች በተካሄደው ውድድር ኬንያዊቷ ሩዝ ቼቢቶክ 2:25:49 ሰዓት ቀዳሚ ሆና ስታጠናቅቅ፤ ኢትዮጵያውያኑ በላይነሽ ፀጋዬ፤ ወርቅነሽ አለሙና አለሚቱ በገና ከቀዳሚዋ አትሌት ከሁለት ደቂቃ በበለጠ ዘግይተው ከሁለት እስከ አራት ያለውን ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል።
በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ዝቅተኛ ደረጃ ባላቸው የጣሊያን ብሬሽያ ማራቶንና የእየሩሳሌም ማራቶን ኬንያውያን ድል ሲቀናቸው፤ የተሻለ ደረጃ ባላቸው የሮም ግማሽ ማራቶንና የፖርቹጋል ሊዝበን ግማሽ ማራቶን ውድድሮች ኢትዮጵያውያን በተለይም በሴቶች መድመቅ ችለዋል። በሮም ግማሽ ማራቶን ሃፍታምነሽ ሃይሉ 1:09:02 በሆነ ሰዓት ቀዳሚ ሆና ስታጠናቅቅ፤ ዴራ ዲዳ 1:09:21 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች። በሊዝበን ግማሽ ማራቶን ደግሞ እታገኝ ወልዱ 1:11:27 በሆነ ሰዓት ቀዳሚ ስትሆን፤ በላይነሽ ኦልጂራ 1:11:29 ሰዓት ሁለተኛ፣ ሔለን ቶላ 1:11:33 ሰዓት ሦስተኛ ሆና ማጠናቀቅ ችላለች።

ቦጋለ አበበ

Published in ስፖርት
Tuesday, 13 March 2018 19:31

ልመና ለሴቶች!

የዚህ ጽሑፍ ርዕስ ‹‹ምክር ለሴቶች›› መባል ሲገባው ዳሩ ግን ነገሩ ከምክርነት ወደ ልመናነት የሚያደላ ስለሆነ ‹‹ልመና ለሴቶች›› ብየዋለሁ፡፡ ተለማኝ ሴቶች ናቸው፡፡ ለማኙስ ማነው? ለሚለው ጽሑፉን ማንበብ ነው (ማን ሊሆን ይችላል ደግሞ ወንዶች ነን እንጂ!) የምር ግን ለማኙ እኔ ነኝ፡፡
ዛሬ ሴቶችን ላደንቅ ነው የተነሳሁት፤ ቅር የሚለው ወንድ ካለ የሴቶችን ብቃት ይለማመድና በቀጣይ ደግሞ እሱን አደንቃለሁ፡፡ እውነቴን ነው ሴቶችን በጣም ላመሰግን ተነስቻለሁ፡፡ ከዚያ በፊት ግን የሰሞኑ ድባብ እንዴት ነበር? የ‹‹ማርች ኤይት›› ድባብ ማለቴ ነው? ኧረ ቆይ አሁንም ወደ ዋናው ጉዳይ ከመግባቴ በፊት ቅሬታ አለኝ፡፡ (ዝም ብሎ አድናቆት ብቻ ይገኛል እንዴ?)
‹‹ማርች ኤይት›› የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል እንዴት አገራዊ ስያሜ አጣ? ቢያንስ ቢያንስ ‹‹መጋቢት ስምንት›› ብንለው እንኳን ምን ነበር? ወይም ደግሞ በዕለቱ በሚውለው የኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር መሰየም አይቻልም? ‹‹ማርች ኤይት›› ምን እንደሆነ የሚያውቁት የተማሩት ብቻ ናቸው፡፡ የሚገርመው እኮ ደግሞ የዚህ ቀን መከበር በዋናነት የትምህርት ዕድል ላላገኙና የጉልበት ብዝበዛ ለሚበዛባቸው ሴቶች ነበር፡፡ ቃሉን የሚያውቁትማ እኮ በዕኩልነት የሚያምኑ ናቸው፡፡ አሁን አንዲት የጉልበት ብዝበዛ የሚበዛባት የገጠር ሴት ‹‹ማርች ኤይት›› ምንድነው ብትባል ምን ትላለች?
ወደ ዋናው ጉዳይ ተመልሰናል፡፡ ዋናው ጉዳይ ምን መሰላችሁ? ባሳለፍነው ሳምንት የሴቶች ቀን ተከብሮ ነበር፡፡ የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ስለሴቶች ብዙ ነገርም ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ (አይዟችሁ እነርሱ ያሉትን አልደግምም)፡፡ ታዲያ እኔስ ለምን የመሰለኝን አልልም? እንደማመጥ እንግዲህ ሴቶች፡፡
ሴቶች ወንድ ማድረግ የማይችለውን ብቃት አላቸው፡፡ የትኛውም የስነ ልቦና ባለሙያ፣ የህክምና ባለሙያ፣ የህግ ባለሙያም ሆነ የጦር ኃይል ማድረግ የማይችለውን ያደርጋሉ፡፡ ይሄ እሙን ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይሄን ማድረግ የቻሉት ግን በሴቶች ጠንካራነት ብቻ ሳይሆን በወንዶች ደካማነትም ጭምር ይመስለኛል፡፡ (ማነህ እንዳትቆጣ)፡፡
ወደ ምክሬ (ልመና በሉት ካሻችሁ) ስገባ ሴቶች እባካችሁ ወንዶችን ልክ አስገቡልን የሚል ነው፡፡ በጣም እውነት ለመናገር ወንድን ልክ የምታስገባው ሴት ናት፡፡ በመሆኑም ወንዶችን ስነ ሥርዓት ለማስያዝ ወንዶች ላይ ከመስራት ይልቅ ሴቶች ላይ መሥራት የተሻለ ነው፡፡ ‹‹ሴት የላከው ጅብ አይፈራም›› የተባለው ዝም ብሎ አይደለም፡፡ ሴቶች በየመድረኩ የሚነገርባቸውን ጎጂ ምሳሌያዊ አነጋገር ሲያወግዙ ‹‹ሴት የላከው ጅብ አይፈራም›› የሚባለውን ግን ልብ አላሉትም፡፡ እነርሱ ደግሞ ችግራቸው ስለሴት እኩልነት ባወሩ ቁጥር ማውገዝ ላይና ሮሮ ላይ ብቻ ማተኮራቸው ነው፡፡
እናም ‹‹ሴት የላከው ጅብ አይፈራም›› ወንድ ለሴት ልጅ በጣም ብዙ ነገር ይሆናል፡፡ አሁን በአገራችን እየታየ ያለው ምስቅልቅል (ለጊዜው ፖለቲካውን አይደለም) የተፈጠረው ሴቶች ያላቸውን ብቃት ስላልተጠቀሙበት ነው፡፡ የባለትዳሮች ወዲያውኑ መፋታት፣ የወንዶች አስረግዞ መክዳት፣ በኑሮ መጨቃጨቅ፣ እርስበርስ ለመጠፋፋት መሞካከር የተፈጠረው በወንዶች ሳይሆን በሴቶች ጥፋት ነው፡፡ ማለቴ ጥፋታቸው ችሎታቸውን አለመጠቀማቸው ነው፡፡ ምክንያቱም ሴት እንኳን የትዳር ጓደኛዋን ሌላውን የማግባባትና ሰላም የማድረግ ችሎታ አላት፡፡ ይህ የሚሆነው ግን በዘዴ ነው፡፡
ቀለል ቀለል ያሉ ምሳሌዎች ላንሳ፡፡ ለብዙ የትዳር መፍረስ ምክንያቱ የወንዶች ጠጪነት፣ አጫሽነት፣ ቃሚነት… ነው፡፡ ይሄ ቀላል ችግር አይደለም፡፡ በቤት ውስጥ አለመስማማትን ያመጣል፤ የባህሪ መነጫነጭን ይፈጥራል፤ በጣም ሲከፋም ስንፈተ ወሲብ ይፈጥራል፣ የዘር መምከንን ያመጣል፡፡ ይሄ ሆኖ ደግሞ ትዳሩ ትዳር አይሆንም፡፡ ሌላው ሱስ ቀርቶ መጠጡ ብቻ ቢሆን እንኳን ከሌላ ሴት ጋር መማገጥን ያመጣል፡፡ ይህም መጠራጠርንና መጨቃጨቅን ይፈጥራል፡፡
ሴት ልጅ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ማስቀረት ትችል ነበር፡፡ አንድ ወንድ የሚወዳት ሴት እንኳንስ ጫትና ሲጋራ ‹‹ምግብ ተው›› ብትለው ይተዋል፡፡ እዚህ ላይ አንድ የማውቀው ገጠመኝ አለኝ፡፡ (የሆነች ልጅ ናት የነገረችኝ፡፡) ልጁ በጣም ይወዳታል፡፡ በግንኙነታቸው ውስጥ ጫት እንደሚቅም ደረሰችበት፡፡ በጣም እንደምትወደውና ጫቱን ካልተወው ግን በፍጹም አብረው እንደማይሆኑና እንዲያውም ለሻይ ቡና እንኳን እንደማታገኘው ነገረችው፡፡ ለአፍታማ ሳያቅማማ ነው ጫቱን እርግፍ አድርጎ የተወው፡፡ ምንም እንኳን አሁን አብረው ባይሆኑም እንደ እህትና ወንድም ይተያያሉ፤ ዛሬ ድረስ ከልብ ያመሰግናታል፤ ያደንቃታልም፡፡ ልጅቷም አብረው እንደማይሆኑ እያወቀች ጫቱን ለማስተው የተጠቀመችው ዘዴ ነበር፡፡ ጎበዝ ሴት ማለት ለኔ እንዲህ ነው፡፡
እዚህ ላይ ይልቅ ትልቁ ችግር አንዳንድ ሴቶች ደግሞ አራዳ የሚባል ወንድ መውደዳቸው ነው፡፡ እነርሱ ‹‹አራዳ›› የሚሉት ደግሞ የሚቅምና የሚያጨስ ነው፡፡ አንድ ወንድ የሚወዳትን ለማግኘት የማያደርገው ነገር የለም፡፡ በአራዳነቴ ትወደኛለች ካለ እንኳንስ ጫት ሌላም ነገር ሊበላ ይችላል፡፡ እርግጥ ነው ይሄ የብዙ ሴቶች ባህሪ አይደለም፤ እውነቱን እናውራ ከተባለ ግን የጀማሪ አራዳ ሴቶች ባህሪ ነው፡፡ በቃ ሱሪውን ዝቅ የሚያደርግ፣ ጸጉሩን የሚጎናጉን፣ የሚቅምና የሚያጨስ ወንድ ይወዳሉ፡፡ ስንቱ ወንድ እኮ የተበላሸው አራዳ የሆነ እየመሰለው ነው፡፡
አብዛኞቹን ሴቶች ካየን ግን መጠጥ፣ ጫትና ሲጋራ የሚጠሉ ናቸው፡፡ ይሄ ሆኖ ሳለ ግን ወንዶች ከዚህ እንዲላቀቁ ጥረት አላደረጉም፡፡ ‹‹ለምን እነርሱ የተለየ ዘመቻ ማድረግ አለባቸው?›› ከተባለ ማስቆም የሚችሉት እነርሱ ስለሆኑ ነው፡፡
በእውነት እስኪ ሴቶች የሚቅምና የሚያጨስን ወንድ ያግልሉና በአንድ ዓመት ውስጥ በአገሪቱ ውስጥ ቃሚና አጫሽ ባይጠፋ! አሥር ሳይንቲስት ‹‹ሲጋራ ገዳይ ነው!›› ከሚል ይልቅ አንዲት ሴት ‹‹ዞር በል አታጭስብኝ›› ብትለው እርግፍ አድርጎ ይተወዋል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር ይባል ይሆናል፡፡ የሚያጨስንና የሚቅምን ሰው ‹‹ዞር በል፣ አታጭስብኝ›› ማለት ነውር ነው፤ ክብር ይነካል ይባል ይሆናል፡፡ ማጨስና መቃም እኮ የፈጣሪ ቁጣ አይደለም፤ ከላይ የወረደ መዓትም አይደለም፤ በራስ መተማመን በማጣት የመጣ ነው፡፡ እስኪ እነዚህ ታዋቂና ተወዳጅ ናቸው የሚባሉት ያውግዙትና በአጭር ጊዜ ውስጥ ባይቆም!
ማንም ትሁን ማን ለምትቀርበው ወንድ ይህን ዘመቻ ብትጀምር ነገሩ ቀላል ነበር፡፡ ማንም ወንድ እንኳን የሚፈልጋትን ሴት የየትኛዋንም ሴት ወሬ ይወዳል፡፡ (አንወሻሽ ጎበዝ!)፡፡ ‹‹አንተ ይሄን ጭስ ይዘህ ሁለተኛ እንዳታናግረኝ›› ብትለው ያፍራል፤ ይተወዋል፡፡ ወንድ እንደዚህ ቢለው ግን ክንዱን ሰቅስቆ ነው ለድብድብ ነው የሚነሳው፡፡
ሴቶች ግን ልብ ብላችሁኛል? ‹‹ትችላላችሁና ወጣቱን ከሱስ አውጡት›› ነው እያልኩ ያለሁት፡፡ በመጠጥ፣ በጫትና ሲጋራ እናንተ የተመሰገናችሁ ናችሁ፤ አትወዱም፡፡ (አጫሽና ቃሚ ሴቶች ቢኖሩም እንደ ወንዶች አይደለምና ብዙዎችን አይወክልም)፡፡ ይሄን ሥራ ሰራችሁ ማለት ቀላል እንዳይመስላችሁ፡፡ ትልቅ አገራዊ ሥራ ነው፡፡ ‹‹እንደ ጫትና ሲጋራን እንደ ትልቅ አጀንዳ ያወራል›› የሚል ካለ ተሳስቷል፡፡ ጫትና ሲጋራ ፖለቲካዊ ጉዳይ ነው፤ ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ነው፤ ማህበራዊ ጉዳይ ነው፤ ከምንም በላይ ደግሞ የጤና ጉዳይ ነው፡፡ ይሄን አስቀራችሁ ማለት እንግዲህ ምን ልበላችሁ! በቃ ሕይወት አዳናችሁ ማለት እኮ ነው፡፡ ተግባባን?
እናም እላለሁ! እባካችሁ ሴቶች ማድረግ ትችላላችሁና ይሄን ቅጠላ በላ ወንድ ልክ አስገቡልን!

Published in መዝናኛ

ዶክተር አታክልቲ ባራኪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና ባለሞያ ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ ሃኪምነት ተከታትለዋል፡፡ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውንም በዚሁ ተቋም በአጠቃላይ ቀዶ ሃኪምነት ስፔሻሊቲ ስልጠና አጠናቀዋል፡፡ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በኖርዌ መንግስት ድጋፍ ለሶስት ዓመታት በኢትዮጵያ፣ በኖርዌይ፣ በህንድና በእንግሊዝ አገር በፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ሰርጀሪ ተከታትለዋል፡፡ በአሜሪካንና በታይዋን አገራትም ከሙያው ጋር የተያያዙ አጫጭር ኮርሶችን ወስደዋል፡፡ በአጠቃላይ ሃኪምነትና በቀዶ ህክምና ባለሙያነት ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ሆስፒታሎች አገልግለዋል፡፡ በፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና ከ16 አመት በላይ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ አሁን ደግሞ በዚሁ ሙያቸው በአለርት ማዕክል እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ የፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና በኢትዮጵያ ስላለበት ደረጃ፣ አስፈላጊነቱና በተለይም ከስጋ ደዌ ህመም ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ የአካል ጉዳቶችን በቀዶ ህክምና እንዴት ማሻሻልና መመለስ እንደሚቻል አዲስ ዘመን አነጋግሯቸው እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና ምንድን ነው?
ዶክተር አታክልቲ፡- የፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና ሁለት አበይት ዘርፎችን የያዘ ነው፡፡ አንደኛው የቁንጅና ቀዶ ህክምና (aesthetic or cosmetic surgery) ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና (non aesthetic or reconstructive surgery) ነው፡፡ የሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምናን ከቁንጅና ቀዶ ህክምና በዋናነት የሚለየውም ይህንን አይነቱን ሕክምና የሚፈልጉ ሰዎች በተለያየ ምክንያት አካላቸውን ያጡ፣ የአካላቸው የመስራት አቅም ያነሰ ወይም የአካልን ቅርፅ የሚያበላሽ ጉዳይ ያጋጠማቸው ናቸው፡፡ በብዙ አገራትም የሚሰራው ይህ አይነቱ የቀዶ ህክምና ነው፡፡ በቁንጅና ቀዶ ህክምና በአብዛኛው የሚስተናገዱት ግን ሙሉ አካል ኖሯቸው የነበራቸውን የፊት ገፅታ ወይም ሌላ የሰውነት አካል በአዲስ መልክ ለማሻሻል ወይም ለመለወጥ የሚደረግ የቀዶ ህክምና አይነት ሲሆን፣ ህክምናውም ውድ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀዶ ህክምናው በኢትዮጵያ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
ዶክተር አታክልቲ፡- የኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና በኢትዮጵያ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለማወቅ በቅድሚያ በአገሪቱ ያለውን የአካል ጉዳተኞች ቁጥር ማወቅ የግድ ይላል፡፡ በቅርብ ጊዜ የተጠኑ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ በኢትዮጵያ 17 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች የተለያዩ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው ተብሎ ይገመታል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ስምንት በመቶ የሚሆኑት አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ይህም ህክምናውን የሚፈልጉ አካል ጉዳተኞች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑንና ይህን ሊያስተናግድ የሚችል ተቋም እንደሚያስፈልግ የሚጠቁም ነው፡፡ የህዝቡ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣት፣ የሰዎች የአኗኗር ዘይቤ በጊዜ ሂደት መለወጥ፣ የኤሌክትሪክ ሃይል እንዲሁም የከተሞች መስፋፋትና እድገትን ተክትሎ የሚፈጠሩ የአካል ጉዳት ችግሮች ህክምናውን የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር እንዲጨምሩ የራሳቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀዶ ህክምናውን ለማድረግ የሚያበቁ ዋና ዋና ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
ዶክተር አታክልቲ ባራኪ፡- ቀዶ ህክምናውን ለማድረግ ከሚያበቁ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ በአካል ላይ አደጋ ሲደርስ ነው፡፡ ሰዎች በተለያየ መንገድ የተለያዩ አደጋዎች በብዛት ይደርስባቸዋል፡፡ ቀዶ ህክምና ከሚያስደርጉ ትልልቅ የህክምና ችግሮች ውስጥ ዋነኛ የሚባሉት የመኪና አደጋ፣ በፋብሪካ ውስጥ የሚገጥም አደጋ፣ ቃጠሎና የመሳሰሉት ሲሆኑ፣ እነዚህም በሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና የሚስተካከሉ ናቸው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ሰዎች በተፈጥሯቸው አብረዋቸው የሚወለዱ ችግሮች (በሽታዎች) ናቸው፡፡ በፊት ላይና በጭንቅላት ላይ የሚከሰቱ በሽታዎች፣ በእጅና በእግር ላይ የሚፈጠሩ ችግሮች፣ በፊት ላይ የሚከሰቱ የተለያዩ ኢንፌክሽኖችና በአንገት፣ በጭንቅላትና በሰውነት ቆዳ ላይ የሚከሰቱ የካንሰር አይነቶችም ቀዶ ህክምናው የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀዶ ህክምናው እንዴትና የት ይካሄዳል?
ዶክተር አታክልቲ፡- ህክምናው በተለይም ስጋደዌን በሚመለከት በአብዛኛው በመንግስት ጤና ማዕከላት የሚሰጥ በመሆኑ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ በአነስተኛ የገንዘብ ወጪ የሚስተናገድ ይሆናል፡፡ ትልቁ የቀዶ ህክምና ክፍያም ከ350 ብር የማይበልጥ ነው፡፡ ይህም በመንግስትና በረጂ ድርጅቶች ድጋፍ የሚደረግለት የህክምና ዘርፍ መሆኑን ያሳያል፡፡ የሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምናን በሚመለከት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመጠኑም ቢሆን በግል ተቋማት ላይ አገልግሎቱ እየተሰጠ ይገኛል፤ ነገር ግን ህክምናው በበቂ ሁኔታ አልተስፋፋም፡፡ የሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ሰዎች አብዛኛዎቹ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙና አቅም ኖሯቸው በግል ህክምና ማድረግ የማይችሉ ከመሆናቸው አኳያ አገልግሎቱን በመንግስት ተቋማት ያገኛሉ፡፡
ህክምናው ረጅም ጊዜ የሚፈጅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደ ሌሎቹ ቀዶ ህክምናዎች ብዙ ሰዎችን በአንድ ጊዜ ማከም አይቻልም፡፡ ሌሎች ተጓዳኝ የህክምና ባለሙያዎችንም በማካተት የሚካሄድ በመሆኑ ከሌሎች ቀዶ ህክምናዎች የተለየ ያደርገዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በስጋ ደዌ ህመም ምክንያት የአካል ጉዳት የሚያጋጥማቸው ሰዎች በቀዶ ህክምናው እንዴት ይስተናገዳሉ?
ዶክተር አታክልቲ፡- የስጋ ደዌ ህመም በዋናነት የነርቭ ችግር ነው፡፡ አንድ ሰው የመጀመሪያውን የህመም ምልክት በሚያይበት ጊዜ ህክምናውን በማግኘት ባክቴሪያውን ማጥፋት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ የነርቭ መቆጣት ሊያጋጥም ስለሚችል አሁንም ወደ ህክምና ቦታ በመሄድ የተቆጣውን ነርቭ ማርገብ ያስፈልጋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ማድረግ ሳይቻል ሲቀር ጡንቻዎች ይላላሉ፤ ስሜት አይኖርም፤ የነርቭ ስርአት የሚቆጣጠረው አካል አይኖርም፡፡ በመሆኑም እንደ አካል ጉዳቱ መጠንና አይነት ታይቶ የቀዶ ህክምናው ይከናወናል፡፡ የእጅና እግር የመስራት ብቃት እንዲሻሻል የተለያዩ ቀዶ ህክምናዎች ይካሄዳሉ፡፡ ጡንቻዎችን የማዟዟር ስራዎች ይሰራሉ፡፡ የተወጠሩ ነርቮች እንዲላሉና እንዲላቀቁ ይደረጋል፡፡ በጡንቻ መላላት ምክንያት የእግር ጣቶችና የእግር ቅርፅ እየተበላሸ ስለሚሄድና ቁስል ስለሚያመጣ በቶሎ የመጡትን ያለ ቀዶ ህክምና እግሮቻቸውን በምን መልኩ መንከባከብ እንዳለባቸው ትምህርት ይሰጣቸዋል፡፡ ከዛ የከፋ የአካል ጉዳት የገጠማቸውን ደግሞ ልዩ ጫማዎች እንዲዘጋጅላቸው ይደረጋል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ ሂደቶችን ካለፈ የተለያዩ አይነት የቀዶ ህክምናዎች ይደረጋሉ፡፡ እነዚህ ቀዶ ህክምናዎች በዋናነት የሚሰሩትም አለርት ማዕከል ላይ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በቀዶ ህክምናው የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣትና ታካሚውን ማርካት ይቻላል?
ዶክተር አታክልቲ፡- በሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና በጣም ትንሽ የሚባሉ ነገሮች በታካሚው ላይ ትልቅ ለውጥ ሲያመጡ ይታያሉ፡፡ በተለይም የስጋ ደዌ ታማሚዎች የእጅ ነርቫቸው ሲቃጠል በእጃቸው እቃ መያዝ አይችሉም፡፡ ይሁን እንጂ ቀዶ ህክምናው ጡንቻዎችን በማስተካከልና በማዟዟር እቃዎችን በእጆቻቸው እንዲይዙ ይደረጋል፡፡ በቀዶ ህክምናው ለውጥ ቢመጣም የተሻለ ለውጥ ለማምጣት ስራው የሚቆም አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት አንድ ታማሚ ለቀዶ ህክምና አምስትና ስድስት ጊዜ ያህል ሊመጣ ይችላል፡፡ ይህም የጎደለው አካሉ የበለጠ እንዲስተካከል ያደርጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ህክምናውን ለመስጠት አስቸጋሪ የሚያደርጉ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
ዶክተር አታክልቲ፡- በዘርፉ የሰለጠኑ ሙያተኞች በበቂ ሁኔታ አለመኖር፣ በቀዶ ህክምና ቡድኑ ውስጥ መካተት የሚገባቸው ተጓዳኝ የህክምና ሙያተኞች ቁጥር አናሳ መሆን፣ የተቋማት ጠንካራ ያለመሆን እንዲሁም ህክምናው በጥቂት ተቋማት ውስጥ መሰጠቱ የህክምናው ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ታማሚዎች ጉዳቱ ሲደርስባቸው በቶሎ ወደ ህክምና ቦታ አለመምጣትም ሌላኛው የህክምናው አስቸጋሪ ገፅታ ነው፡፡ የመጀመሪያ የአካል ጉዳተኝነት ምልክት ደረጃ ላይ የሚደረገው ቀዶ ህክምና የከፋ የአካል ጉዳት ከመድረሱ በፊት ለማቆም ያስችላል፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ ደረጃ ካለፈ የዚያኑ ያህል የቀዶ ህክምናውን አስቸጋሪና ውስብስብ ያደርገዋል፡፡ በተቋም ደረጃ በአለርት ማዕከል የስጋ ደዌ የቀዶ ህክምናን ለማካሄድ በቂ መሳሪያ ያለ ቢሆንም፤ በሌሎች አገልግሎቱ በሚሰጥባቸው ተቋማት ግን በበቂ ሁኔታ አይገኝም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀዶ ህክምናውን በበቂ ሁኔታና በሚፈለገው መጠን ለመስጠት መፍትሄው ምንድን ነው?
ዶክተር አታክልቲ፡- በማዕከሉ ህክምናውን ፈልገው የሚመጡ ሰዎች አንድም ችግሩ ኖሮባቸው የሚመጡ አሊያም አዳዲስ ታማሚዎች ናቸው፡፡ አዳዲስ ታማሚዎች በተቻለ መጠን ምንም አይነት የአካል ጉዳት እንዳይደርስባቸው ህክምና እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ የቀዶ ህክምናውን የሚሰጠው ተቋምና ባለሙያዎች ቁጥር ውስን በመሆኑ የቀዶ ህክምናውን በበቂ ሁኔታና መስጠት አልተቻልም፡፡ በጊዜው ለማስተናገድም አልተቻለም፡፡ ይህንንም ለማሻሻል በርካታ ስራዎች መስራት አለባቸው፡፡ ተቋማትም መስፋፋት ይኖርባቸዋል፡፡ መንግስት በተለይም የስጋ ደዌ የቀዶ ህክምና አገልግሎቱ የሚሰጥባቸው ተቋማት ተቀናጅተው እንዲሰሩ ቢያደርግም፤ በየቦታው ያሉ ተቋማትና የህክምና ባለሙያዎች ህክምናውን እንደሚሰጡ ማረጋገጥ ላይ ሰፊ ክፍተት ይታያል፡፡ ይህን ክፍተት ማሟላት የሚቻል ከሆነ ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና ከመደረሱ በፊት መከላከል ይቻላል፡፡ የጤና ባለሙያዎችን የስጋ ደዌ ህክምናን ማሰልጠን የሚቻል ከሆነም ትንንሽ ቁስሎችን እዛው ማከም ይቻላል፡፡ በሌሎች ቦታ ላይ የሚገኙ ተቋማት ህክምናውን እየሰጡ ቢሆኑም፤ ያላቸው አቅም ደካማ በመሆኑ ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ እዛ ቦታ ላይ ያሉ ባለሙያዎችንም ማብቃት ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ህክምናውን አስመልክቶ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ይኖር ይሆን?
ዶክተር አታክልቲ፡- ፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህከምናን አስመልክቶ በህብረተሰቡ ዘንድ ብዥታ እንዳይኖር ግንዛቤ ማስጨበጥ ያስፈልጋል፡፡ ህክምናው አስፈላጊ በመሆኑም በተሻለ ሁኔታ ተጠናክሮ እንዲሰጥ ሊሰራበት ይገባል፡፡ በጊዜያዊነት በርካታ ችግሮች ያሉበት የህክምና ዘርፍ ቢሆንም በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር የሚሰጡ ስልጠናዎች እየተስፋፉ ሲሄዱ ህክምናውን በተሻለ መልኩ መስጠት ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ፍቃደኛ ሆነው ለሰጡኝ ሙያዊ ማብራሪያ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ስም አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር አታክልቲ፡- እኔም አመሰግናለሁ

አስናቀ ፀጋዬ

Published in ማህበራዊ
Tuesday, 13 March 2018 17:03

የተስፋው ወጋገን

‹‹ህዝብ አይሳሳትም በጅምላም አይፈረጅም›› ይህ መንግስት ለበርካታ ዓመታት ህዝባዊነት በአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ያለውን ፋይዳ ከሚገል ፅባቸው መንገዶች አንዱ ንግግር ነው፡፡ታዲያ ከአስርት ዓመታት ቀደም ብሎ ፖሊሲና ስትራቴጂዎቹን ሲያወጣ ህዝባዊነቱ ላይ በአንክሮ እየተመለከተ ነበር፡፡በተለይም በመልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ ስርዓት በሚለው ሰነድ ላይ የህዝብን ተሳትፎ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ካልተቻለ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ዕድገት ለማስመዝገብ አገሪቱን ካለችበት ጥልቅ የድህነት ጉድጓድ ለማውጣት አዳጋች እንደሚሆንባት ተዳሷል፡፡ ለዚህም መነሻ የሚሆኑ የመልካም አስተዳደር እንዲሁም ኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮች ተለይተው ማድረቂያ ስልታቸውም ተነድፎ እንደነበር ከሰነዶቹ መረዳት ይቻላል፡፡
በፖሊሲና ስትራቴጂዎቹ ችግሮቹ ተለይተው መፍትሄ ቢቀመጥላቸውም ዳሩ ግን በአሁኑ ወቅት መነሻቸውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ያደረጉ ሁከት የተቀላቀለባቸው ድርጊቶች ሲፈፀሙ ይስተዋላል፡፡ መንግስትም በተለያዩ ወቅቶች የህዝብን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እየለቀመ በመያዝ እንዲፈቱ እያደረገ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ እየሰራ መሆኑን ገልጧል፡፡ ለዚህም ችግሮችን ሳያፈናጥር ወደራሱ በመውሰድ በጥፋት ውስጥ የነበሩ ህዝብን በድለዋል የተባሉ አካላትን ተመጣጣኝ የእርምት እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ይገልፃል፡፡ በተመሳሳይ ህዝቡንም ይቅርታ በመጠየቅ ከህዝቡ ጋር የጋራ መግባባት በመፍጠር ለተሻለ ለውጥ እንደሚሰራ ቃል ገብቷል፡፡
እኛም በተለያዩ ወቅቶች ተገልጋይ ይበዛባ ቸዋል፣ ከችግር ያልወጣ ዘርፍ እንዲሁም ለኪራይ ሰብሳቢነት ዋነኛ ምንጭ ነው ተብሎ ከተለየው መሬት ጋር በተያያዘ ቅኝት ልናደርግ ወደድን፡፡ በዚህም ከዚህ ቀደም በዘርፉ የነበሩ መረጃዎች፣ በአሁኑ ወቅት ተገልጋዮች ምን ይላሉ? በሚልና ከኃላፊዎች ጋር ያደረግነውን ቆይታ እነሆ፡፡
መነሻ ሁኔታ
በ2009 ዓ/ም በጥልቅ ተሃድሶ የተለዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማቃለል የተዘጋጀው ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት እንደሚያመላክተው፤ ከክልሎች ውጪ ሚኒስቴሩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተመረጡ ተቋማት ላይ በለውጥና መልካም አስተዳደር አፈፃፀም ላይ ክትትልና ድጋፍ አድርጓል፡፡ከተመረጡት ተቋማት መካከልም መሬት ልማት ማኔጅመንት አንዱ ነው፡፡በክትትልና ድጋፉም የመልካም አስተዳደር ችግሮች አለያየትና እቅድ አስተቃቀድ፣የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባርና አመለካከት አለያየትና እቅዱ እንዴት መታቀድ እንዳለበት፣ የዜጎች ቻርተርን፣ የተገልጋዮችም ሆነ የውስጥ ሰራተኞች የእርካታ ደረጃ እንዴት መጠናት እንዳለበት ተገንዝቦ መስራት ላይ ክፍተት ያለበት መሆኑ ታይቷል፡፡
በከተማው የክትትልና ድጋፍ በተደረገባቸው ተቋማት አመራሩ የለውጥና መልካም አስተዳደር ስራዎችን ትኩረት ሰጥቶ ከመስራት አንጻር በደራሽ ስራዎች ስለሚያዝ በሚፈለገው ደረጃ ከመደገፍ አንጻር ክፍተት እንዳለበት ታይቷል፡፡ በተያያዘ የውስጥና የውጭ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በአግባቡ በመለየት ከማቀድና በወቅቱ ከመፍታት፣ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባርና አመለካከት ምንጮችን ከመለየትና ትግል እያደረጉ ከመሄድ፣በተቀመጠው የዜጎች ቻርተር አማካኝነት አገልግሎት ከመስጠትና ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ እያስጨበጡ ከመሄድና የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በአግባቡ በመያዝና በመፍታት፣ የህዝብ ክንፉን በአግባቡ በመለየትና አቅሙን በመገንባት ተሳትፎው እንዲጨመር ከማድረግ አንጻር ክፍተት እንዳለ ሪፖርቱ በዝርዝር ያስቀምጣል፡፡
በሚኒስቴሩ በተዘረጋው የዜጎች የቅሬታና አቤቱታ አፈታት ስርዓት ከፌዴራል፤ ከክልሎች፣ ከከተማ አስተዳደሮችና ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት የመጡ ባለጉዳዮች ያቀረቡት ቅሬታና አቤቱታ ምላሽ እንዲያገኙ በማድረግ የዜጎች እርካታን ለማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች ሲከናወኑ እንደቆዩ የስራ አፈፃፀሙ ያብራራል፡፡ከዚህ አኳያ በበጀት ዓመቱ ከዜጎች የቀረቡ ቅሬታዎችና አቤቱታዎች ይዘት ሲታይ በተለይ ከመሬት ይዞታ መብትና ካሳ አከፋፈል ጋር የተያያዙና መሰል ችግሮች እንደሚታዩ ማስቀመጡ ይታወሳል፡፡
ለትውስታ
በቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት በአንድ ወቅት በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ያነጋገርናቸው ተገልጋዮች እንደተናገሩት፤ ጉዳያቸው በወቅቱ አይፈፀምም፡፡ ምንም እንኳ አገልግሎቱን ለማግኘት የሚፈጀው ጊዜ በስታንዳርድ ተለክቶ ቢቀመጥም ዕውነታው ግን ከዚህ ውጪና ከሰዓት አልፎ የወራቶች ዕድሜን ይፈጃሉ፡፡ በተለይ‹‹ስራ ላይ የሉም ስብሰባ ላይ ናቸው››የሚሉ የተለመዱ ምላሾች ህብረተሰቡን ለምሬት፣ እንግልትና ለቅሶ ዳርገውታል፡፡ከህዝቡ እየተከፈላቸው ተጨማሪ ጥቅምን ከራሱ ህዝብ የሚፈልጉ አካላት ተጠያቂ ቢደረጉና መንግስት ራሱን ቢፈትሽ የተሻለ ይሆናል፡፡
በፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር የፌዴራልና የክልሎች የመልካም አስተዳደር ክትትልና ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በላቸው ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በአንድ ወቅት በሰጡን መረጃ የ2009 በጀት ዓመት የመልካም አስተዳደር ዕቅድ ጥራት ያለውና የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ መመለስ የሚችል ሆኖ እንዲዘጋጅ ተደርጓል፡፡ በዚህም የክትትልና ድጋፍ ሥራው ውጤት እንደሚያሳየው የመልካም አስተዳደር ዕቅድ በማቀድ ደረጃ ጥሩ ቢሆንም የተለዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በብቃትና በጥራት ስራዎችን በማከናወን ማቃለል፣የተፈቱና ያልተፈቱትን በአግባቡ ለይቶ መረጃ የመያዝ፣በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት አገልግሎት መስጠቱን የመለየት፣በለውጥ ሠራዊት ማኑዋል በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ከሕዝብ ክንፉ ጋር ከመገናኘት አንጻር በየደረጃው በታዩ ተቋማት ላይ ውስንነት እንደሚስተዋልና በቀጣይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም መታየቱን አስረድተው ነበር፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ይስሐቅ ግርማይ በበኩላቸው በተያዘው 2010 በጀት ዓመት የተደረገው ጥልቅ ተሃድሶ ለችግሮቹ መፈጠር ዋነኛ ምክንያት በአገልግሎት ሰጪው ዘንድ ህዝብን በቅንነት የማገልገል አመለካከት ሙሉ በሙሉ አለመያዙ መሆኑን መግለፃቸው ይታወሳል፡፡ከዚህ ቀደምም መንግስት ችግሮችን ለማቃለል በስፋት ቅሬታ የሚነሳባቸው ተቋማትን በመለየት አቅዶ ሲሰራ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ሃላፊው እንዳብራሩት የከተማ አስተዳደሩን የ2009 በጀት ዓመት አፈጻፀም መነሻ በማድረግ በተያዘው 2010 ዓ.ም ምን መሰራት እንዳለበት በሰፊው የሚዳስስ ዕቅድ ተዘጋጅቷል፡፡ ምንም እንኳን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የሁሉም ጉዳይ ቢሆንም በርካታ ተገልጋይን የሚያስተናግዱት እንደ መሬት ያሉ ተቋማት ትኩረት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህም መሰረት የከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ ተቋማት በተለዩት ከ3 ሺህ 600 በላይ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ኃላፊው አመላክተዋል፡፡_ ህብረተሰቡም የሚያነሳቸውን ችግሮችም በቀሪ ወራት ለማቃለል በልዩ አቅጣጫና ርብርብ እየሰሩ መሆኑን የገለፁ ሲሆን እኛም በተባለው ልክ እየተሰራ ስለመሆኑ ከተገልጋዩ ልናደምጥ ወደድን፡፡
ተገልጋዩ ምን ይላል?
ከቦሌ ክፍለ ከተማ አገልግሎት ፈልገው በአራዳ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የመሬት ይዞታ ምዝገባ መረጃ ኤጀንሲ ያገኘነው ተገልጋይ ወጣት ምናለ ሰንደቁ ነው፡፡ወጣቱ በጽህፈት ቤቱ በተገኘበት ዕለት ባልጠበቀ ሁኔታ አገልግሎቱን ማግኘቱና ያለእንግልት መጨረሱ እርካታ እንደሰጠው በደስታ ይናገራል፡፡‹‹እንደዚህ ዓይነት አሰራር አይቼ አላውቅም›› በማለት ቀድሞ በተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ቢሮዎች ሲሄድ የነበሩት ችግሮች አሁን አለመኖራውን ይገልፃል፡፡
ባለሙያዎቹ ተገልጋይን ተቀብለው ከሚያስተናግዱበት ትህትና የተሞላበት መንገድ ጀምሮ አገልግሎት አሰጣጣቸው ከዚህ ቀደም ከነበረው አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ሲነፃፀር ለውጡ ግርምትን እንዳጫረበትም ወጣት ምናለ ይገልፃል፡፡በዚህም ፈፃሚዎቹ ሁሉም ተጋግዘው ተገልጋዩ የመጣበትን ጉዳይ ጨርሶ እንዲሄድ ማድረግ እንጂ ባለሙያው የለም በሚል ስለማይመልሱ ይህ ፈጣን ምላሽ ለማግኘት አስችሎታል፡፡ምልልስ ቀርቶ ባለጉዳዩ እንዳይቆምም አድርጎታል በማለት የመጣውን ለውጥ ያመላክታል፡፡ይህም ቀድሞ ህብረተሰቡ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ይነሱ የነበሩ ችግሮችን ለማቃለል የሚኖረው ሚና ጉልህ ይሆናልና ይቀጥል ባይ ነው፡፡
እኛም በወቅቱ በጊቢው ምንም ዓይነት ተገልጋይ ማጣታችን ቢያስገርመን መሻሻሉ በአንድ ክፍለ ከተማ የታጠረ ወይንስ ሌሎችም ጋር ይኖር ይሆን? በሚል ከቦሌ ከፍለ ከተማ ወጥተን ወደ የካ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት አመራን፡፡በጽህፈት ቤቱ መግቢያ በር ላይ የሁሉም አገልግሎት ሰጪዎች ስም ዝርዝር ከኃላፊው ጀምሮ የሚሰጡት አገልግሎት የሚገልፅ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር ተመለከትን፡፡ወደ ውስጥ ስንዘልቅም በተመሳሳይ ሁሉም ተገልጋይ ለተገልጋይ በተዘጋጁ መቀመጫዎች ተቀምጦ ከፊት ለፊቱ ያለውን የቴሌቪዥን መስኮት ሲመለከት አስተዋልን፡፡ ቴሌቪዥኑ ልክ ውጪ ላይ እንዳለው ቴክኖሎጂ ተመሳሳይ ቢሆንም ይህ ደግሞ ተገልጋዮች በስም ዝርዝራቸው ጉዳያቸውንና ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ በግልፅ ያሳያል፡፡ይህም ደንበኛው ጉዳዩ እንደተፈፀመለትና እንዳላለቀለት የሚያመላክት ጭንቅንቅን የሚቀንስ ከመሆኑም በላይ ተገልጋዩ ጉዳዩ ካላለቀለት ምን እንደሚጎ ድለው አውቆ ወደሚመለከተው አካል በመሄድ ቀጣይ እርምጃውን የሚያመላክትም ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ከሌሎች ክፍለ ከተሞችም በክፍለ ከተማው ያለውን የተሻለ አሰራር ልምድ ለመቅሰም የተገኙ በርካታ ባለሙያዎችን ተመልክተናል፡፡
በጽህፈት ቤቱ ያገኘናቸው ተገልጋይ አቶ ወርቄ ቸርነት ከክፍለ ከተማው ወረዳ 11 ነዋሪ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ከዚህ ቀደም የነበረው የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ሙሉ በሙሉ ለባለሙያዎቹ የሚተው ሳይሆን የአደረጃጀት ችግር እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡ከዚህ ውጪም አገልግሎቱን ለማግኘት ለስድስት ጊዜያት ያክል እንደተመላለሱና መሀንዲስ እንደወሰዱ የሚናገሩት ነዋሪው ችግሩ ከአደረጃጀት ውጪም ዘርፉ ለኪራይ ሰብሳቢነት ተጋላጭ በመሆኑ ትኩረት እንደሚሻ አመላካች ነው፡፡በጽህፈት ቤቱ በርካታ ተገልጋይ ቢኖርም የሚያስተናግደው የሰው ሀይል ውስን መሆኑ ግን ለችግሮቹ መነሻ ነበር የሚሉት አቶ ወርቄ በንፅፅር በአሁኑ ወቅት ተገልጋዩንና አገልጋዩን ብሎም ስፍራውን ምቹ መደረጉ ለለውጡ ምክንያት ነው ይላሉ፡፡መዝገብ ቤቱ ሁለት ተደርጎ ለተገልጋዩ ምቹ ለማድረግ የተሰራው ስራ አበረታች ገፅታ ቢኖረውም አሁንም ባለሙያዎችን ለስህተት የሚዳርጉ ቀዳዳዎችን ለመድፈን መሰራት ይገባል፡፡
እንደ አቶ ወርቄ ገለፃ፤የመሬት ጉዳይ በባህሪው እጅግ ከባድና ለብልሹ አሰራር ተጋላጭ በመሆኑ ትኩረት ሊነፈገው አይገባም፡፡ባለሙያዎቹ ተከታታይ የሆነ ስልጠና መስጠት በተያያዘም ታዛቢ የሆነ አካል በጽህፈት ቤቱ እየተገኘ ቢጎበኝ የተሻለ ይሆናል፡፡ስራውንም የተሳካ ለማድረግ ኃላፊዎችም ለተገልጋዩ ቢሯቸውን ክፍት አድርገው የሚነሱ ጥያቄዎችን ይዘው እየወረዱ እንዲፈታም እያደረጉ መሆናቸው ውስጣቸውን በሀሴት ሞልቶታል፡፡
በቅርብ ጊዜያት መንግስት ራሱን እንደፈተሸና ለውጥ እንደሚመጣ ያስቀመጠው አቅጣጫም እየታየ ላለው ለለውጥ አዎንታዊ አስተዋፅዖ እንዳበረከተ አቶ ወርቄ አይጠራጠሩም፡፡ይህንን መነሻ በማድረግ በቅርብ በክፍለ ከተማው እየተፈጠረ ያለው ህዝባዊ የውይይት መድረክም ችግሮችን ቀርፈዋልና የተጀመረው አሳታፊነትና ግልፅነት የተሞላበት አሰራር ቀጣይነት ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ በተያያዘ ክፍለ ከተማ ላይ ብቻ የተንጠለጠሉ ስራዎች ወደ ወረዳ ቢወርዱና ተገልጋዩ በአካባቢው አገልግሎቱን እያገኘ ጊዜውንም ጉልበቱንም ቢቆጥብ ጅማሮው የተሻለ እንዲሆን ያደርገዋልና ቢታሰብበት መልካም እንደሆነ አመላክተዋል፡፡በአሁኑ ወቅት ቀድሞ እርሳቸው ሲመላለሱ የነበሩበት ችግርና የሌሎች ተገልጋዮችም ችግር ተለይቶ መፍትሄ እንዲሰጠው መደረጉን መመልከታቸው መንግስት በአሁኑ ወቅት ለህዝቡ ቃል በገባው መሰረት ለለውጥ መነሳቱን አመላካች ነው፡፡
በጽህፈት ቤቱ ያገኘናቸው ሌላኛዋ እናት ወይዘሮ አበበች ዘውዴ በክፍለ ከተማው የካ አባዶ አካባቢ ነዋሪነታውን ያደረጉ ተገልጋይ መሆናቸውን ነገሩን፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ጉዳያቸው ባለመ ፈፀሙ ምክንያት ለሰባት ዓመታት ውሳኔ ሳያገኙ ለጥያቄያቸውን ተገቢው ምላሽ ሳይሰጣቸው ተንከራተዋል፡፡ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ተለውጠው እንደመጡ ከከተማ ከንቲባ ድረስ ተወያይተው ችግራቸው እንዲፈታ ሆኗል፡፡ ይህም የሚያመላክተው ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ችግሮች ለማቃለል የአመራር ቁርጠኝነትና ህዝባዊነት ምን ያክል ለውጥ አምጪ እንደሆነ ትልቅ ማሳያ ይሆናል፡፡በተመሳሳይ ለበርካታ ዓመታት ከችግራቸው ጋር ሲመላለሱ ሳይፈታላቸው ሲንከራተቱ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ለ12 ዓመታት የተመላለሱ ሌሎች ተገልጋዮችን አስተዋውቋቸዋል፡፡ እነርሱም በተመሳሳይ ሁኔታ ለረጅም ዓመታት መፍትሄ ያልተሰጠው ችግራቸው እልባት ተሰጥቶታል፡፡
ያለምንም መጉላላት በአሁኑ ወቅት ያሉት ኃላፊ ጉዳያቸው እንዲፈፀም ማስቻላቸው የበርካታ ዓመታት እንባቸውን እንዳፈሰላቸው ወይዘሮ አበበች ይናገራሉ፡፡ተመሪም መሪውን ይመስላልና ባለሙያዎቹም ለባለጉዳይ የሚያደርጉት መስተንግዶ እጅጉን ተሻሽሏል፡፡በመሆኑም መንግስት ቅድሚያ መገንባትና መመልከት የሚገባው የአመራር ብቃት ላይ ነው፡፡ይህን መሰል የህብረተሰቡን ጥያቄ እያዳመጡ ፈጣን ምላሽ የሚሰጡ የስራ ኃላፊዎች ቢበራከቱ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እየታየ ያለው ፍጅትና እልቂትም አይኖርም ነበር በማለት የችግሮቹ ዋነኛ ተጠያቂ አመራሩ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በመሆኑም መንግስት በአሁኑ ወቅት የጀመረውን የለውጥ ጉዞ አጠናክሮ ለመቀጠል በመንግስት የስራ ኃላፊነት ላይ ያሉ አካላትን መፈተሸ ይኖርበታል ይላሉ፡፡
አገልግሎት ሰጪዎች
በአራዳ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የመሬት ይዞታ ምዝገባ መረጃ ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ መኮንን እንደሚያስረዱት ከስድስት ወራት በፊት በርካታ ችግሮች ነበሩ፡፡የአገልግሎት አሰጣጥ የስራ ፍሰት የመሳሰሉ የስራን ቅልጥፍናን የሚያፋጥኑና የተገልጋዩን እርካታ የሚያረጋግጡ አሰራሮች አልተዘረጉም ነበር፡፡ጉዳዮችም በአንድ ቋት የነበረ በመሆኑ ተገልጋዩን ለእንግልት ሲዳርጉት ቆይተዋል፡፡
አገልግሎት ፈላጊው ወደ ቢሮው ሲመጣ ኃላፊው እንዲመራ ይጠበቃል፡፡ይህም ኃላፊው በስብሰባና በመሰል ጉዳዮች ሳይገኝ በሚቀርባቸው ጊዜያት ባለጉዳዩ ጉዳዩ ሳይፈፀምለት ለቀናት ለምልልስ ይዳረጋል፡፡በመሆኑም ችግሩን ከለየ በኋላ መፍትሄዎችና አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል፡፡ በዚህም የስራ ፍሰቱ ተጠብቆ እንዲሰራ ተደርጓል፡፡በዚህም ስራዎች ከአገልግሎት መስኮት ተገልጋዩ አስፈላጊውን መረጃ ይዞ በመጣበት ወቅት ሁሉ አገልግሎቱን ማግኘት እንዲችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ለዚህ እንዲያመችም መስኮቶችን የመከፋፈል ስራ ተሰርቷል፡፡
በፋይል አወጣጥ ላይ በክፍለ ከተማው በሁሉም ወረዳዎች በአንድ ሰው ብቻ ይሰጥ የነበረው አገልግሎት አሰጣጥ ለሶስት በመክፈል የፋይል አወጣጡ ፍጥነት ማሳደግ ተችሏል፡፡ከዚህ ጋር ተያይዞ በየቀኑ ወደ ጽህፈት ቤቱ የሚመጡ ጉዳዮችን በትኩረት የማየት አሰራር ተዘርግቷል፡፡በዚህ አሰራርም እያንዳንዱ ጉዳይ በየዕለቱ ምን ደረጃ እንደደረሰ ክትትል ይደረግበታል፡፡ይህም ተገልጋዩ ጉዳዩ እንደተፈፀመለት አልያም ካልተፈፀመ የት ቦታ ላይ እንደታነቀ በቅርቡ በማወቅ ለእያንዳንዱ ችግር ከመነሻው መፍትሄ እያበጁና የተገልጋዩን እርካታ ለማስጠበቅ እየተሰራ መሆኑን አቶ ብርሃኑ ይጠቁማሉ፡፡ለአብነት ቀድሞ በአንድ ወር ውስጥ 49 ብቻ ካርታ የተሰጠ ሲሆን ችግሩን የማጥራትና አገልግሎቱ የት ቦታ ላይ እንደታነቀ የልየታ ስራ ተሰርቷል፡፡በዚህም አለአግባብ ካርታዎች ይታነቁበት የነበረውን ቦታ በማወቅ ሰራተኞቹን አቅርቦ ከማነጋገር እስከ እርምት እንዲወሰድ ተደርጓል፡፡
ችግሮችን በመለየትና የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ ሂደት ውስጥም የተሻለ ለውጥ እንደመጣ በአንድ ወር ውስጥ በተሰራ ስራ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ማሻሻያዎች ከተደረጉ በኋላ 150 ካርታ በመስጠት አገልግሎቱን በሶስት ዕጥፍ ማሳደግ ተችሏል፡፡ ይህም አገልግሎቱን በማሻሻል ቀድሞ ከህብረተሰቡ ይነሱ የነበሩ ችግሮችን ትርጉም ባለው ደረጃ ተቃሏል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቀድሞ በሰፊው በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ይነሱ ከነበሩ ችግሮች መካከል አንዱ መረጃ አሰጣጥ ጉድለት ነው፡፡ አገልግሎት ፈላጊ ወደ ጽህፈት ቤቱ ሲያመራ ጉዳዩ ምን እንደሆነ አውቆና ተረድቶ የት መሄድ እንዳለበት ብሎም ምን ማሟላት እንደሚገባው የሚያስገነዝብ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ላይ ችግሮች ይስተዋሉ ነበር፡፡ ይህንንም ችግር ለማቃለል መግቢያ በር ላይ መረጃ የሚሰጥ አካል ሙሉውን መረጃ ሰጥቶ በማስቀመጥ ተገልጋዩ ገና ከበር ሲገባ ጉዳዩ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰለት ማወቅ የሚያስችለው አሰራር ተዘርግቷል፡፡ በዚህ የመጣውን ለውጥ ለማወቅም የተገልጋይ እርካታ በየጊዜው እየተመዘነና ማሻሻያም እየተደረገ ነው፡፡
አሰራሩን ለማስቀጠል ትንቅንቅ ውስጥ በመግባት ጭምር እየተሰራ እንደሆነም አል ሸሸጉም፡፡ አዲስ አሰራር ሲሰራ ከሰራተኞች የሚነሳ ችግሮችና ማነቆዎች ይኖራል በማለት በለውጥ ሂደት ውስጥ አዲስ አሰራርን ላለመቀበል የሚሻ አካል እንዳለ ይጠቁማሉ፡፡ እኛም ለውጥን ያለመፈለጉ ችግር ትክክለኛ ምንጩ ከወደየት ይሆን? ስንል ጥያቄያችንን አነሳንላቸው፡፡ ኃላፊውም በምላሻቸው ለውጥን ላለመቀበል የሚፈጠረውን ትንቅንቅ ከሚፈጥሩ ምክንያቶች አንዱ የአቅም ማነስ ነው ይላሉ፡፡በስራ ላይ ውሳኔ የሚሹ ጉዳዮችን ፈጣን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ሌላ አካል የመጠበቅ ዝንባሌዎች ሲኖሩ አመራሩም ተከታትሎ የማሰራት ችግሮች መኖራቸውን ያምናሉ፡፡
ዘርፉ ለኪራይ ሰብሳቢነት ተጋላጭነቱ ሰፊ በመሆኑም ይህንን ትኩረት ሰጥቶ ከመስራት ጋር ተያይዞ ያለበት ደረጃስ ምን ይመስል ይሆን በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ለኪራይ ሰብሳቢነት ምቹ የሆኑ መንገዶችን የማጥበብ ስራ መሰራቱን አቶ ብርሃኑ ያስረዳሉ፡፡ይሁን እንጂ ችግሩ በሁሉም ስፍራ ላይ በሚፈለገው ደረጃ ለማቃለል ያልተቻለበት ምክንያት ማህበረሰቡም በጉዳዩ ላይ ያለው አቋም ክፍተት ያለበት መሆኑን ሳይናገሩ አላለፉም፡፡በዚህም አንዳንድ ተገልጋዮች መብታቸው እንደሆነ አውቀው አገልግሎትን በትክክለኛ መንገድ ከማግኘት ይልቅ በብልሹ አሰራርና ለሌሎችም ተገልጋዮች የአገልግሎት አሰጣጡን በሚያበላሽ መልኩ ባለሙያዎችን በጥቅማጥቅም ሲደልሉ ይታያል፡፡ በመሆኑም ችግሩን በሚፈለገው ደረጃ ለማቃለል ህዝብ ከመንግስት ጋር ሆኖ የሚሰራቸው ስራዎች ለውጥ አምጪ መሆናቸውን በመገንዘብ ንቁ ተሳትፎና ትግል ማድረግ ይገባል ይላሉ፡፡
የየካ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግደይ አለምሰገድ እንደሚናሩት፤በጽህፈት ቤቱ ስር አራት ጽህፈት ቤቶች የሚገኙ በመሆኑ በርካታ ተገልጋዮች የሚጎርፍበት እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይህንንም ለማስተካከል ቅድሚያ ተገልጋዩን በምን መልኩ ማርካት ይቻላል? በሚል ከሰራተኞች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ በውይይቱም በሶፍትዌር ዕውቀት የነበራቸው ባለሙያዎች አሰራን በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን ለማስቻል እንደሚሰሩ ኃላፊነቱን ወሰዱ፡፡በዚህም የተገልጋዩን እንግልት የሚቀንሱ ስራዎችን ለጽህፈት ቤቱ ማበርከት ቻሉ፡፡
አዲሱ አሰራር መረጃ በቀላሉ ማግኘት የሚያስችልና አገልግሎት ጠያቂው ጉዳዩ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ በማን እንደሚስተናገድና ወረፋውን ጠብቆ በወቅቱ አገልግሎቱን እንዲያገኝ ያስችለዋል፡፡ በተመሳሳይ ማህደሮችም እንግልት በሚቀንስ መልኩ እንዲወጡና ጥራታቸውም እንዲጠበቅ ያስችላል፡፡ አገልግሎቶች በተቀመ ጠላቸው ስታንዳርድ መሰረት እንዲሰጡና ይህንን ያላደረገ አካል ተጠያቂ እንዲሆን የተጀመሩ ስራዎች እንዳሉም አቶ ግደይ ያስረዳሉ፡፡
አቶ ግደይ እንደሚያስረዱት፤ ህዝቦች በወቅቱ አገልግሎት የማግኘት መብት አላቸው፡፡ መንግስትም ህዝባዊ በመሆኑ ይህንን መሰረት ያደረጉ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ተቃሏል ማለት አይቻልም፡፡ አሁንም እንግልቶችና በአንዳንድ ባለሙያዎች የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር እንዳለ ህብረተሰቡ ያነሳል፡፡ጽህፈት ቤቱም ይህንን ተቀብሎ ምክር ከመስጠትና የህዝብ አገልጋይነት አመለካከት ከማስረፅ ባለፈ ተመጣጣኝ የእርምት እርምጃን ይወስዳል፡፡ በዚህም ስድስት ባለሙያዎች ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ሲሆን ሁለት ደግሞ በተጨባጭ ሲደራደሩ ተገኝተዋል በሚል በመጣ ጥቆማ ከፖሊስ ጋር በመተባበር በህግ እንዲጠየቁ ተደርጓል፡፡ ይህም ቀጣይነት እንዲኖረው የህብረተሰቡ ያላሰለሰ ጥረት መጠናከር ይገባዋል፡፡
ቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ
በአሁኑ ወቅት በዘርፉ የነበሩ ችግሮችን ለይቶ አሰራር ዘርግቶ እየተሰራ ቢሆንም ስራው ግን በዘላቂነት ለማስቀጠል ጠንካራ አመራር ይፈልጋል የሚሉት ዳይሬክተሩ ጽህፈት ቤቱ ይህን ታሳቢ ያደረጉ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በቀጣይም መሰረተ ልማቶች የተሳለጡ እንዲሆኑ ማስቻል ዋናው የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነም ይገልፃሉ፡፡ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ከታቀደ ለዚህ መሳካት ከኔትወርክ መቆራረጥ ጋር ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮች በተመሳሳይ መብራት ላይ ያሉ የሀይል መቆራረጦችንና መሰል ችግሮችን ከሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት ለመፍታት እቅድ ተይዟል፡፡
የጥራት ጉዳይ ሌላው በችግር የነበረ መሰረታዊ ጉዳይ በመሆኑ ጽህፈት ቤቱ ይህንን መነሻ ያደረገ የትኩረት አቅጣጫ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አቶ ብርሃኑ ይገልፃሉ፡፡ በተሟላ ዕውቀትና በክትትል ማነስ የተበላሹ ስራዎች እንደነበሩም ያስታውሳሉ፡፡ ይህንንም ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ እየተሰራባቸው ነው፡፡ ስራው በሶስት ወረዳዎች የተጀመረ ሲሆን 58 የህዝብ ታዛቢዎች ተመርጠዋል፡፡ በዚህም ጥራት ሲሰራ እንዲታዘቡና ስራው የህብረተሰቡ አካል ሆኖ የጥራት ማስጠበቁ እንዲሳካ የተጀመረው ስራ እንዲቀጥል ይሰራል፡፡
በዘርፉ በአገልግሎት አሰጣጥ እየታየ ያለው ለውጥ ክትትሉ ስታንዳርዱን እንዲያስጠብቅ ማድረግ ማስቻል ሌላው የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ይሆናል፡፡ተገልጋዩ የሚፈልገው አገልግሎት በተቀመጠለት የጊዜና ጥራት ወሰን ውስጥ እንዲከናወን ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡ ለዚህም የስራ ፍሰቱን መመልከት፣ የሰው ሀይል መሟላት፣ የተሟላ ዕውቀትና ምቹ የስራ ቦታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ባለሙያው ከሰበብና ከግላዊ ፍላጎት ፀድቶ በህዝባዊነት መንፈስ ወገኑን በቅንነትና በታማኝነት እንዲያገለግል የተለያዩ መድረኮች ላይ የማስረፅ ስራ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ ይህም ግለሰቦች ባይኖሩም በተዘረ ጋው ምቹ አሰራር መሰረት ተገልጋዮች በስታንዳርዱ መሰረት የሚስተናገዱበትና ከዚህ ውጪ ከሆነም ጥያቄያቸውን የሚያቀርቡበት ሁኔታን በመፍጠር ቀድሞ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የነበረውን ችግር በሰፊው ያቃልላል ለዚህም ህብረተሰቡ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅበታል ይላሉ፡፡
እንደ አቶ ግደይ ገለፃ፤የተጀመሩትን መልካም ተግባራት ለማስቀጠል ሰራተኛው የህዝብ አገልጋይነት ስሜቱን ለመገንባት ተከታታይ ስልጠና ይሰጣል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ግብዓት የማሟላት፣ በቅንነትና በታማኝነት እንዲሁም ስነምግባር በተሞላበት መንገድ እንዲሰሩና የሰሩትን የማበረታታት፣በተለይ በአሁኑ ወቅት በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር እንዲኖር ያስቻሉትን ባለሙያዎች የማበረታታትና ስራቸውን እንዲያሳድጉ የመደገፍ፣ አገልግሎቱንም በሁሉም በማስፋት ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት ይሰራል፡፡

ፍዮሪ ተወልደ

Published in ፖለቲካ

ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የሚደረገውን ሽግግር በረዥም ጊዜ ሂደት እውን ለማድረግ እንዲሁም በአፍሪካ ቀዳሚ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማእከል ለመሆን እየሰራች ትገኛለች። የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንትን ከማስፋፋት ጎን ለጎን የኢንዱስትሪ ግብአት አቅርቦት ማረጋገጥ ሌላኛው የቤት ሥራ በመሆኑ እኩል ትኩረት እና ሰፊ ጥረት ይፈልጋል። ለዚህም ሲባል መንግስት በ2006 ዓ.ም በቀድሞ የሸቀጦች ጅምላ ንግድ እና አቅራቢ ድርጅት ወይም ጅንአድ ላይ የተልእኮና ስያሜ ለውጥ በማድረግ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት ተብሎ እንዲቋቋም ማድረጉ ይታወቃል። የድርጅቱ የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ሥራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ታዬ ድርጅቱ ስለተቋቋመበት ተልእኮ፣ወቅታዊ አፈፃፀምና ስላሉበት ችግሮች ከአዲስ ዘመን ጋር ያደረጉትን ቃለ-መጠይቅ ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት ሲቋቋም የተሰጡትን ዓበይት ተልእኮዎችንና ለዘርፉ ያበረከተውን ጠቀሜታ ቢያብራሩልኝ ?
አቶ መላኩ፡- መንግስት ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር የሚደረገው መዋቅራዊ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ግንባር ቀደም የሆነች አገር ለመፍጠር እና ማኑፋክቸሪንግ በአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚጫወተውን ሚና ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል። በመጀመሪያውም ሆነ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ዋነኛው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማነቆ የግብአት እጥረት ነው። ብቸኛው ችግር ግን አይደለም። ስለዚህ ዘርፉ በአለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዳይሆን የግብአት እጥረት ቁልፉ ማነቆ እስከሆነ ድረስ መንግስት ችግሩን ከመሰረቱ ይፈታልኛል ብሎ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ድርጅትን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 328/2006 መሠረት የመንግስት የልማት ድርጅት ሆኖ እንዲዋቀር አድርጓል።
ይህ ድርጅት ከተሰጡት ተልእኮዎች መካከል አንዱ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የኢንዱስትሪ ግብአቶችንና ውጤቶችን በማቅረብ፣ የግብአት አቅርቦትን ለማረጋገጥ የሚረዱ ፕሮጀክቶችን በማልማትና በማስተዳደር፣ በማስተላለፍ በተፈጥሮ ሃብትና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአሰራር ስርዓት በመተግበር ተወዳዳሪና ውጤታማ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ እንዲፈጠር ድጋፍ ማድረግ ነው። የአቅም ውስንነቱ አሁን ያንን ለማከናወን የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ ለመፍጠር ባያስችለንም፤ድርጅቱ ግብአቶችን ገዝቶ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ራሱ ግብአቶችን በማልማት ኢንዱስትሪዎችን የመደገፍ ሚናም የተሰጠው ተቋም ነው። ኢንዱስትሪዎችን ተጠቃሚ ሲያደርግ፥ግብአት አቅራቢውንም አካል ጎን ለጎን ተጠቃሚ አድርጓል።
ድርጅቱ በዋናነት የሚያቀርባቸው የኢንዱስትሪ ግብአቶች የግብርና ውጤቶች ናቸው፡፡ በዚህም ግብርና መር ኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂውን ይደግፋል። እንደ ማሳያ ጥጥን ብንወስድ ከዚህ በፊት ምርቱ ዋጋው ሲወርድ አምራቹ አርሶ አደር በሚቀጥለው የምርት ወቅት ጥጡን አቁሞ ወደ ሩዝ ይሸጋገር ነበር። አሁን ድርጅቱ አርሶና አርብቶ አደሩ ያመረተውን ምርት የሚሸጥበት የማይነጥፍ ገበያ ስለፈጠረለት ሳያቋርጥ ማምረቱን ይቀጥላል። ግዥና ሽያጭ የምንፈጽመው ወቅታዊውን የዓለም አቀፍ ገበያ የምርት መሸጫና መግዣ ዋጋ ታሳቢ አድርገን ስለሆነ የሚያመርተው አካል በቀጥታ ተጠቃሚነቱ ከፍተኛ ይሆናል። ከፍተኛ ትሥሥርም ፈጥሯል። ቀደም ሲል አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የሚያመርተውን ጥጥ ለአቅራቢዎች ሲሸጥ በነበረበት ወቅት፣ምርቱ ወደ ኢንዱስትሪዎቹ በጥራትና በፍጥነት እንዳይደርስ ያደርግ የነበረው አሉታዊ ተጽእኖ ተቃሏል።
አዲስ ዘመን፡- ድርጅቱ በዋናነት የሚያቀር ባቸው የኢንዱስትሪ ግብአቶችን ይጥቀሱልኝ ?
አቶ መላኩ፡-የኢንዱስትሪ ግብአት ስንል መንግስት ቅድሚያ የሰጣቸው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ግብአቶች በመሆናቸው ቅድሚያ ከሰጣቸው ዘርፎች ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ሲሆን ለዘርፉ የሚሆኑ ግብአቶች በተለይ ጥጥ፣እንዲሁም ጥሬ ቆዳና ሌጦ፣ለኢንዱስትሪ ምርት የሚውል ጨው ይጠቀሳሉ። አሁን ዘግይተን ደግሞ ለአግሮ ኢንዱስትሪ ፕሮሰሲንግ የሚያስፈልጉ ግብአቶችንም ማቅረብ ጀምረናል። በእነዚህ ብቻ ላለመታጠር ደግሞ ኬሚካልና አክሰሰሪዎችን (ተጓዳኝ እቃዎችን) ለማቅረብ ከሚመለከታቸው የዘርፍ መስሪያ ቤቶች ጋር በመቀናጀት ጥናት አጥንተን ቅድመ ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡-ድርጅቱ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ለኢንዱስትሪ ግብአት ምን ያህል ወጪ አውጥቷል ? ምን ያህል የግብአቶች መጠንስ አቅርቧል ?
አቶ መላኩ፡- ድርጅቱ ከ 2007 እስከ 2009 ዓ.ም በጀት ዓመት ድረስ ወደ 899 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ ግብአቶችን ለኢንዱስትሪዎች አቅርቧል። በ2010 በጀት ዓመት ያለፉት ሰባት ወራት ብቻ ወደ 258 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ዋጋ ያለው ግብአት ማቅረብ ችሏል። በአጠቃላይ ድርጅቱ ከተቋቋመ በኋላ አንድ ነጥብ 16 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ የኢንዱስትሪ ግብአቶች 22 ለሚሆኑ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ማቅረብ ችለናል።
አዲስ ዘመን፡-የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት የተቋቋመበት ካፒታል ምን ያህል ነበር ?
አቶ መላኩ፡-ድርጅታችን ሲቋቋም የተፈቀደለት ካፒታል 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ ጅንአድ ውስጥ የነበረ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር አስቀድሞ ተከፍሏል። ቀሪው አልተከፈለም።
አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ የኢንዱስትሪ ግብአቶችን ከየት እየገዛ ያቀርባል? ከአገር ውስጥ ወይስ ከውጭ ?
አሁን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ ግብአቶችን የምናቀርበው በዋነኛነት ከአገር ውስጥ ገዝተን ነው፤ነገር ግን በዚህ ብቻ አይታጠርም፥አገር ውስጥ የሌለ ግብአት ከሆነ ከውጭ የማንገዛበት ምንም ምክንያት የለም። ኬሚካሎችና አክሰሰሪዎች እና ሌሎች የኢንዱስትሪ ግብአቶችን ማቅረብ ስንጀምር ወደ ውጭ ገበያ እንገባለን።
አዲስ ዘመን፡-ድርጅቱ የኢንዱስትሪ ግብአት የሚያቀርበው ለሃገር ውስጥ ፋብሪካዎች ብቻ ነው?
አቶ መላኩ፡-ግብአቶችን ለኢንዱስትሪዎች ስናቀርብ በዋነኛነት የምናተኩረው የወጪ ንግድ መር የኢንዱስትሪ ልማት አቅጣጫውን የሚደግፉ አምርተው በወጪ ንግድ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ኢንዱስትሪዎችን ቅድሚያ እንሰጣለን። ስለዚህ የአገር ውስጥ የውጭ ባለሃብት ብለን ሳንለይ ለሁሉም ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ ይህን ስንል አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን እንዘነጋቸዋለን ማለት አይደለም።ባሉን የመሸጫ ማእከላት እና ቅርንጫፎች ጥሬ ቆዳና ሌጦ እንዲሁም ከፊል ያለቀለት የቆዳ ውጤቶች እናቀርብላቸዋለን።
አዲስ ዘመን፡-ድርጅቱ በተያዘው በጀት ዓመት ወደ ውጭ የላካቸው የኢንዱስትሪ ግብአቶች አሉ?
አቶ መላኩ፡- አሁን ተልእኳችን ግብአቶችን ወደ ውጭ መላክ አይደለም።በአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች በቂ ግብአት አግኝተው ችግራቸው ተቀርፏልም ማለት አይቻልም።ስለዚህ የኢንዱስትሪ ግብአት ወደ ውጭ አላክንም።
አዲስ ዘመን፡- የልማት ድርጅት እንደመሆኑ መጠን በዚህ ጊዜ ውስጥ ካቀረበው የኢንዱስትሪ ግብአት ምን ያህል ትርፍ አግኝቷል ?
አቶ መላኩ፡- ተቋሙ ትልቁ የተቋቋመበት ግብ ትርፍ ሳይሆን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን የግብአት ችግር ከመሠረቱ መፍታትና ዘርፉ በአለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን የሚያስችል ድጋፍ ለመሥጠት ነው። ተቋሙ የኢንዱስትሪውን ችግር ለማቃለል የተቋቋመ ተጠሪነቱ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሆነ የልማት ድርጅት ነው።
አዲስ ዘመን፡-ድርጅቱ የተሠጠውን ኃላፊነት እንዳይወጣ ያደረጉትና ትኩረት ሊሠጥባቸው የሚገባ ማነቆዎችን ቢያብራሩልኝ ?
አቶ መላኩ፡-በተወሰነ ደረጃ የኢንዱስትሪ ግብአት እጥረት ችግርን ማቃለል ችለናል። ነገር ግን፤አሁንም የኢንዱስትሪ ግብአት ችግር ሙሉ በሙሉ ተቃሏል ብለን አናስብም። ተቋማችን የተሰጠውን ተልእኮ በተሟላ ሁኔታ እንዳይፈፅም ካደረጉት ችግሮች ትልቁ ለድርጅቱ ማቋቋሚያ የተፈቀደው ካፒታል ባለመለቀቁ፣በሃብት ውስንነት የሚገደብ ተቋም አድርጎታል። እኛ የግብአት ግዢ አከናውነን ለኢንዱስትሪዎች በስድስት ወር የመመለሻ ጊዜ ተዋውለን በዱቤ ሽያጭ እናስተላልፋለን። አሁን ባለው አዝማሚያ አብዛኞቹ ኢንዱስትሪዎች በዱቤ ከወሰዱ በኋላ በውላችን መሠረት ክፍያ አይፈፅሙም። ይሄ በድርጅቱ አቅም ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሯል። የወሰዱትን በተባለው ባለመመለሳቸው ወደ ህግ እያቀረብናቸው ያሉ ድርጅቶችም አሉ፡፡ ሌላ ድርጅቱ አዲስ ተልእኮ የተሰጠው እንደመሆኑ መጠን ወደ ፊት ሊያራምድ የሚችል መዋቅራዊ አደረጃጀት ፈጥረናል። ነገር ግን ዘርፉ ብቁ ሙያተኛ የሚፈልግ ስለሆነ፤ የሰው ሃይል በሟሟላትና በማብቃትና ስትራቴጂ የማዘጋጀት ሂደት ላይ ነን።
አዲስ ዘመን፡- የድርጅቱን የማስፈጸም አቅምን እየተፈታተኑ ያሉት ችግሮች እንዲፈቱ እያደረጋችሁት ያለው ጥረት ምን ይመስላል ?
አቶ መላኩ፡- ያልተከፈለው የመቋቋሚያው ካፒታልን በተመለከተ ጥያቄያችንን ለመንግስት አቅርበን መፍትሔ እየጠበቅን ነው። ብድር ወስደው እዳቸውን በወቅቱ ባለመመለሳቸው ያጋጠሙን ችግሮችን ከባለሃብቶችና ባለሃብቶቹን በቀጥታ ከሚደግፉ የዘርፍ መስሪያ ቤቶች ጋር በመሆን ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረግን ነው። የሰው ሃይል ችግርን ለመፍታትም ይህንን ተልእኮ ሊሸከም የሚችል አዲስ አደረጃጀት ነው የሰራነው። አደረጃጀት መሥራት በራሱ ግብ ስለማይሆን ዘርፉን የሚስፈልገውን ሙያተኛ ይዘን ለመንቀሳቀስ አዳዲስ የሙያ ስብጥሮችም አካተናል።

በሪሁ ብርሃነ

Published in ኢኮኖሚ

የሰላሳ ሁለት ዓመቱ ወጣት የሳኡዲ ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሃመድ ቢን ሰልማን ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በሙስና የተጠረጠሩ የመንግስት ባለስልጣናትን ማሰራቸው ይታወሳል፡፡ የሳዑዲ አረቢያ ከፍተኛ የጦር መሪዎችንም መቀየራቸው እንዲሁ፡፡ የፀረ ሙስና ዘመቻቸውን ይበልጥ በማጠናከርም ሚኒስትሮችንና ተፅዕኖ ፈጣሪ ቱጃሮችን ከያሉበት በማደን በቁጥጥር ስር እንዲውሉም አድርገዋል፡፡
ይህ ድርጊታቸው ምናልባትም ስልጣናቸውን በይበልጥ ለማመቻቸትና ተቀናቃኞቻቸውን ጥግ እንዲይዙ የረዳቸው ሳይሆን እንዳልቀረ ተንታኞች ይገልፃሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በጠንካራ የሼሪያ ህግ የምትመራውን አገራቸውን ሳዑዲ አረቢያን ዘመናዊነት እንድትላበስ የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎችን አድርገዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያዘም በተለይ ሴቶችን የሚከለክሉ ህጎችን እንዲሻሩ አድርገዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ሴቶች በሳዑዲ ጎዳናዎች ላይ መኪና እንዲያሽከረክሩና ስታዲየም በመግባት የእግር ኳስ ጨዋታዎችን እንዲመለከቱ ፍቃድ መስጠታቸውም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ሲኒማ ቤቶች በአገሪቱ እንዲከፈቱም ይሁንታቸውን ቸረዋል፡፡
ልዑል አልጋ ወራሹ ሳዑዲ አረቢያን ማስተዳደር ከጀመሩ ወዲህ የመጀመሪያ የሆነውን ዓለም አቀፍ ይፋዊ የስራ ጉብኝታቸውን ባለፈው ሳምንት ለሶስት ቀናት በእንግሊዝ አድርገዋል፡፡ በርካታ የመገናኛ ብዙኃን የልዑል አልጋ ወራሹን የእንግሊዝ ጉብኝት ‹‹መንታ ገፅታን የተላበሰ›› ሲሉ ገልፀውታል፡፡ አንድም የእንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት መነጠልን ተከትሎ ሳዑዲ አረቢያ የአገሪቱ ጠንካራ አጋር ሆና ትቀጥላለች ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ሳዑዲ አረቢያ ዓመታትን ባስቆጠረው የየመን ግጭት በተለይም የሁቲ አማፅያን ላይ በምትወስደው ተደጋጋሚ ጥቃት የንፁሃን ዜጎችና የህፃናት ህይወት በመቀጠፉ በርካቶች ጉብኝታቸውን የተቃወሙ መሆኑን ነው፡፡
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ፤ አልጋ ወራሹ እንግሊዝ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው የሳዑዲ አረቢያ መሪ ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ ሳዑዲ አረቢያ የእንግሊዝ የረጅም ጊዜ አጋር ሆና ስለቆየች ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት አባልነት የምትነጠል ከሆነ የሳዑዲ አረቢያና የእንግሊዝ ግንኙነት አዲስ ቅርፅ በመያዝ ይቀጥላል የሚል ግምት በመኖሩም ነው፡፡ ሳዑዲ አረቢያ በተለይም በደህንነትና መከላከያ ዙሪያ ከእንግሊዝ ጋር ያላት ግንኙነት ጠንካራ ነው፡፡ በመሆኑም የአልጋ ወራሹ ጉብኝት የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደተሻለ ምዕራፍ ሊያሸጋግር ይችላል፡፡
‹‹ወጣቱ ልዑል አልጋ ወራሽ በአገራቸው ሳዑዲ አረቢያ የጀመሩትን የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ማሻሻያዎች ለማጠናከር እንዲረዳቸው ዓለም አቀፍ ድጋፍ ለማሰባሰብ የእንግሊዝ አገር ጉብኝታቸው አንዱ ጅማሪያቸው ነው›› ሲል ቢቢሲ በዘገባው አመልክቷል፡፡ በተጓዳኝም የውጭ አገር ኢንቨስተሮችን ወደአገራቸው ለመሳብም ጭምር የታለመ ጉብኝት እንደሆነ ነው ያብራራው፡፡ በአክራሪ የሼሪያ ህግ የምትተዳደረውን ሳዑዲ አረቢያ ወደ ዘመናዊነት ለመለወጥ ልዑል አልጋ ወራሹ የሚያደርጉትን ጥረት ደግሞ እንግሊዝ በእጅጉ ትደግፈዋለች ሲል ቢቢሲ አስታውቋል፡፡ ልኡል አልጋ ወራሹ የሊበራል እስልምናን ለማራመድ ካላቸው ፅኑ ፍላጎትና አገራቸውን እ.ኤ.አ በ2030 ነዳጅ ላይ ጥገኛ የሆነውን ኢኮኖሚ ወደ ሰፊ የገበያ ተኮር ኢኮኖሚ ለመለወጥ ራዕይ አስቀምጠው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህን ራዕያቸውን በማሳካት ረገድ አገራቸው ከእንግሊዝ ጋር የሚኖራት ግንኙነት ወሳኝ ነው፡፡ ይህን በማሳካቱ ሂደት ጉብኝቱ ሰፊ ፋይዳ የነበረው መሆኑንም ዘገባው ያስረዳል፡፡
እንግሊዝ በሳዑዲ አረቢያ በትምህርት፣ ጤና፣ መዝናኛና የቱሪዝም ቢዝነስ ማስፋፊያ ስራዎች ከሳዑዲ አረቢያ የተሻለ ብልጫ አላት፡፡ ከሳዑዲ አረቢያ የአገር ውስጥ ያልተቆጠበ የቀጥታ ኢንቨስትመንትም እንግሊዝ ተጠቃሚ ሆናለች፡፡ የወጣቱ ልዑል አልጋ ወራሽ ጉብኝት፤ በተለይም የእንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት አባልነት መነጠልን ተከትሎ አገሪቱ በገበያና በገንዘብ የሌሎች አገራትን ድጋፍ ስለምትሻና ሳዑዲ አረቢያ ደግሞ ለዚሁ ድጋፍ በእንግሊዝ ከሚፈለጉ አገራት ዝርዝር ውስጥ በመሆኗ ይህ ለሁለቱ አገራት በተለይም ለእንግሊዝ ወሳኝ አጋጣሚ ነው፡፡ የሁለቱ አገራት አዲስ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት በተለይም በኢንቨስትመንት ልውውጥ ረገድ እስከ 76 ቢሊዮን ፓውንድ ለማድረስ የታለመ እንደሆነም ዘገባው አብራርቷል፡፡
ሁለቱ አገራት የሚለያዩባቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳሉም ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡ የእንግሊዝ መንግስት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለውን የየመንን መንግስት ለመመለስ ሳዑዲ መራሹ የጥምር ኃይል በሁቲ አማፅያን ላይ እየወሰደ ያለውን ወታደራዊ ርምጃ በመርህ ደረጃ የሚደግፈው ቢሆንም፤ የሳዑዲ መንግስት የሚወስደው ወታደራዊ የኃይል ርምጃ ትክክለኛና ተመጣጣኝ ባለመሆኑ የበርካታ ንፁሃን ዜጎች ህይወት ተቀጥፏል፡፡ ይህም የእንግሊዝ መንግስትን በእጅጉ እንደሚያሳስበው ቢቢሲ ተንታኞችን በመጥቀስ ዘግቧል፡፡ ለዚህም ይመስላል ልዑል አልጋ ወራሽ መሃመድ ቢን ሰልማን እንግሊዝ ሲደርሱ በዳውኒንግ ጎዳና ሰፊ ተቃውሞ የገጠማቸው፡፡
የሰሞኑን የልዑል የአልጋ ወራሹን የእንግሊዝ ጉብኝት አስመልከቶ አልጀዚራ በበኩሉ እንደዘገበው፤ ብዛት ያላቸው ተቃዋሚዎች ‹‹በየመን ያለው ግጭት ይቁም! ሳዑዲ አረቢያ ከየመን እጇን በአስቸኳይ ታውጣ! ልዑል አልጋ ወራሹ ይታሰሩ! እንግሊዝ ለሳዑዲ አረቢያ የምታደርገውን የመሳሪያ ሽያጭ አሁኑኑ ታቁም!›› የሚሉና ሌሎች የተቃውሞ ድምፆችን አሰምተዋል፡፡
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ በሪቶንስ የመን የተከሰተው ግጭት እንዲቆም በመሻት በኦን ላይን ፊርማ በማሰባሰብ ጠቅላይ ሚኒሰትር ቴሬሳ ሜይ ልዑል አልጋ ወራሽ መሃመድ ቢን ሰልማን የሚያደርጉት የእንግሊዝ ጉብኝት እንዲሰረዝ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘገባው ሲቀጥልም፤ የህፃናት አድን ድርጅትና ዩኒሴፍ ባወጡት መረጃ መሰረት ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ሳዑዲ መራሹ ጥምር ኃይል በየመን ሁቲ አማጽያን ላይ በወሰደው ወታደራዊ እርምጃ ከ110 ሺ በላይ ህፃናት ተገድለዋል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ግን የእንግሊዝ መሳሪያ አምራች ኩባንያዎች የሳዑዲ አረቢያ መንግስት ከ2015 ጀምሮ በተለይም በሁቲ አማጽያን ላይ በሰነዘራቸው ጠንካራ ጥቃቶች የዋሉ የጦር መሳሪያዎችን በመሸጥ ስድስት ቢሊዮን ፓውንድ ገቢ በማግኘት ከውጊያው ተጠቃሚ እንደሆኑ ዘገባው ያመለክታል፡፡
የዳውኒንግ ጎዳና ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ የ90 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት በሁለቱ አገራት መካከል ተደርጓል፡፡ የጦር መሳሪያ ሽያጭ የስምምነቱ አንድ አካል ስለመሆኑ ግን በግልፅ የተቀመጠ ነገር የለም፡፡ ስምምነቱ ሳዑዲ አረቢያ በእንግሊዝ የምታደርገውን የቀጥታ ኢንቨስትመንት ያጠቃልላል፡፡
በህፃናት አድን ድርጅት የሰብአዊ መብት ፖሊሲ ኃላፊ የሆኑት ጀምስ ዴንስሎው ‹‹ሳዑዲ አረቢያ በየመን እየወሰደች ያለው ወታደራዊ እርምጃ ትልቅ ሰብአዊ ጥፋት ነው›› ሲሉ ለአልጀዚራ ገልፀዋል፡፡ በየመን 11 ሚሊዮን የሚጠጉ ህፃናት አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸውም ጠቅሰው፤ ይህ ቁጥር ከቤልጂየም የህዝብ ብዛት በላይ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ለዚህ ችግር ቁልፍ ሚና የምትጫወተው ሳዑዲ አረቢያ ናት›› ሲሉም አገሪቱን ኮንነዋል፡፡
በእንግሊዝ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ጀርሚ ኮርባይን፣ ሳዑዲ አረቢያ በየመን እየወሰደችው ያለውን ወታደራዊ እርምጃ የእንግሊዝ መንግስት ባለማውገዙ ቴሬሳ ሜይን ይወቅሳሉ፡፡ እንግሊዝ ለሳዑዲ በምትሽጥላት የጦር መሳሪያ ምክንያትም የንፁሃን ዜጎች ህይወት እየተቀጠፈ በመሆኑ ቴሬሳ ሜይን ‹‹የጦር ወንጀለኛ›› ሲሉ ይከሳሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ በበኩላቸው፤ ‹‹ሳዑዲ አረቢያ የሚያጋጥሟትን በርካታ ጉዳዮች ለማቅለል መንግስታቸው የመሪነቱን ሚና ይጫወታል›› ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ የሳዑዲ አረቢያው ልዑል አልጋ ወራሽ መሃመድ ቢን ሰልማን በበኩላቸው፤ ‹‹በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ንግድ ለማጠናከር ትልቅ እድል አለ፤ በመካከለኛው ምስራቅ ሽብርተኝነትንና ፅንፈኛ ድርጅቶችን ለመዋጋት አብረን እንሰራለን›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
‹‹እንግሊዝ ለሳዑዲ አረቢያ በምትሸጣቸው የጦር መሳሪያዎች ትርፋማ እየሆነች ቢሆንም፤ ሳዑዲ አረቢያ በነዚሁ መሳሪያዎች በመታገዝ በምትወስደው ወታደራዊ ርምጃ ምክንያት የንፁሃንን ዜገጎች ህይወት እቀጠፈች በመሆኑ የሰብአዊ መብት ጉዳይ የተረሳ ይመስላል›› ሲሉ በቤድፎርድ ዩኒቨርሲቲ የሰላም ትምህርት ክፍል ፕሮፌሰር ፓውል ሮጀርስ ይገልፃሉ፡፡
የእንግሊዝ መንግስት ለሳዑዲ አረቢያ የሚያደርገውን የመሳሪያ ሽያጭ አስመልክቶ በበርካታ የእንግሊዝ የፖለቲካ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ትችት እየገጠመው መሆኑንም አልጀዚራ ጠቅሷል፡፡ ኬት ኦሳሞር የተሰኙትና የሻዶ ኢንተርናሽናል ዴቨሎፕመንት ፓርቲ ፀሃፊ ሁለቱ አገራት ያደረጉትን ጊዜያዊ ስምምነት ‹‹ስህተት›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ቴሬሳ ሜይ የሳዑዲውን ልዑል አልጋ ወራሽ መሃመድ ቢን ሰልማን አገራቸው በንፁሃን ላይ እየወሰደች ያለውን ወታደራዊ እርምጃ እንዲያቆሙ ቅስቀሳ ከማድረግ በዘለለ ትርጉም ያለው ስራ አልሰሩም›› ሲሉም ይተቻሉ፡፡
ጥቂቶች፣ ልዑል አልጋ ወራሹ አክራሪ የህብረተሰብ ክፍል ባለበት ሳዑዲ አረቢያ በፍጥነት እያደረጉ ያሉትን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ማሻሻያዎች በበጎ እየተመለከቱት አይደለም፡፡ ሌሎች ደግሞ ልዑል አልጋ ወራሹ በፀረ ሙስና ዘመቻቸው እየወሰዱት ባለው ርምጃ በተለይም የውጭ ኢንቨስተሮችን በማስደንገጡ ጉዳዩ አሳሳቢ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ በየመን ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ በአጠቃላይ እንግሊዝ ለሳዑዲ ካቀረበቻቸው ልዩ ልዩ የጦር መሳሪያዎች ሽያጭ ስድስት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ፓውንድ ገቢ በማግኘት ካዝናዋን ስታደልብ፤ ከዚህ በተቃራኒ ግን ሳዑዲ መራሹ ጥምር ኃይል በየጊዜው በሚወስዳቸው የአየር ላይ ጥቃቶች አሁንም የንፁሃን ዜጎችን ህይወት እተቀጠፈ ነው፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

Published in ዓለም አቀፍ

የኢህአዴግን አበቃቀልና የአስተዳደግ ባህል በአጽዕኖት ለተመለከተው፣ ኢህአዴግ ጸረ-ህዝብና ጸረ-ዴሞክራሲያዊ ሊሆን የሚችል ፓርቲ አይደለም። ምክንያቱም ኢህአዴግ የወለደው ጭቆና እና ብሶት ነው። ኢህአዴግ መሰረተ ሰፊ ህዝባዊ ድጋፍ ያለው ፓርቲ ነው። በእኛ፣ ከእኛ፣ ለእኛ የሆነ ፓርቲ በመሆኑ ነው። እውነት እውነቱን እንነጋገር ካልን ኢህአዴግ ለአገራችንና ለህዝብ የለውጥ መሰረት አልሆነምን? ኢትዮጵያ ማስመዝገብ ለቻለቻቸው ዘርፈ ብዙ ስኬቶች መሃንዲስ ኢህአዴግ አይደለምን? በአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲፈነጥቅ ፊት አውራሪ አልነበረምን? ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በራሳቸው እንዲኮሩና ራሳቸውን እንዲቀበሉ እንዲሁም ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ የማይተካ ሚና አልተጫወተምን? በአገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ የኢህአዴግ አስተዋጽዖ ወሳኝ አልነበረምን? ኢህአዴግ በዓለም ዓቀፉ መድረክ አገራችን አዲስ ገጽታ እንድትላበስ አላደረገምን?
በእርግጥ በአገራችን በርካታ ችግሮች አሉ። ሁሉም ችግሮች ግን በኢህአዴግ የተከሰቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አይደሉም። ኢህአዴግ በራሱ የፈጠራቸው ችግሮችም ቀላል የሚባሉ እንዳልሆኑ እስማማለሁ። ይሁንና ለሁሉም ችግሮች ግን ምንጩ ኢህአዴግ እንዳልሆነ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። አንዳንድ ግለሰቦች የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ሁሉንም ችግሮች ከመልካም አስተዳደር ጉድለት ጋር ለማስተሳሰርና ኢህአዴግን ለማሳጣት የሚያደርጉትን ሩጫ ስመለከት አፍራለሁ። በመንግስት የአቅም እጦት መንገድ ያልተዘረጋላቸው ወይም ውሃና ኤሌክትሪክ ያልቀረበላቸው አካባቢዎች የመልካም አስተዳደር ችግር ተደርጎ መወሰድ የለበትም ባይ ነኝ።
ለአገራችን የሚበጃት ሁሉንም ችግሮች በየፈርጁ ብንመለከታቸውና በጋራ ሆነን መፍትሄ ብንፈልግላቸው እንጂ በነውጥና ሁከት መፍትሄ እናመጣለን በማለት የበሬ ወለደ ፖለቲካ ለአገራችንም ሆነ ለህዝብ የሚበጅ አካሄድ አይሆንም። ሁሉንም ነገር ወደ ኢህአዴግ መወርወር ኢህአዴግ ራሱ መፍትሄ ይፈልግ ማለት ተገቢ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ኢህአዴግም የእርሱ ጥፋት የሆነውንም ያልሆነውንም የእኔ ጥፋት ነው ብሎ ጠቅሎ መውሰድ አይገባውም። ኢህአዴግ ለሁሉም ችግሮች መፍትሄ ሊያመጣ ከቶ አይቻለውምና።
መልካም አስተዳደር ማስፈን የዕለት ተግባር አይደለም። ሁለም ችግሮች ዕለቱን መፍትሄ አያገኙም። የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማቃለል መንግስት ወይም ገዥው ፓርቲ የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ ላይ ናቸው። ይሁንና ሁሉም ችግሮች በአንዴ መፍትሄ ሊያገኙ አይችሉም። የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍትሄ የሚያገኙት በሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥረት እንጂ በገዥው ፓርቲ ጥረት ብቻ የተፈለገው ውጤት ሊመጣ አይችልም።
በየትኛውም መስክ ለጥፋት ኃይሎች የሚሆን ምቹ ምህዳርን ማሳጣት አንዱ የመንግስትና የገዥው ፓርቲ ተግባር መሆን መቻል ይገባል። የተሰጣ ቸውን ህዝባዊ አደራ መወጣት የማይችሉና ህዝባዊ ድጋፍ የሌላቸው፣ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ አልፎ አልፎ ደግሞ ድብቅ የጥፋት ኃይሎች ፖለቲካዊ ተልዕኮ ይዘው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ኃይሎችን በፅናት መታገል ያስፈልጋል። ህዝቡ የነውጥና የሁከት ጋሻጃግሬዎች እነማን እንደሆኑ ጠንቅቆ ያውቃል። በመሆኑም እነዚህን አካላት ለህግ አሳልፎ መስጠት ይጠበቅታል።
ለአገራችን የሚበጃት፣ ለችግሮቻችን መፍትሄ መፈለግ ያለብን በሰከነና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ ሲሆን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር የፊት ለፊት ውይይት በማድረግ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሚያስችሉ በርካታ መድረኮችን በማድረግ ላይ ነው። የአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ጅምር ቢሆንም፤ መነጋገርና መወያየት የሚያስችል ፖለቲካዊ ምህዳር አለ። ይህን መልካም ጅምር ልንጠቀምበት ይገባል። መስማማት ወይም አለመስማማት አንድ ነገር ሆኖ፤ ቁጭ ብሎ መነጋገር መቻል በራሱ የመጀመሪያውና ትልቁ መልካም ነገር ነው። ጤነኛ የሃሳብ ልዩነት የዴሞክራሲ ስርዓት መገለጫ ነውና።
የጥበትና ትምክህት ሃይሉ የጽንፈኛው የዳያስፖራ ሚዲያዎችንና ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም አገር እንዳበቃላት አድርገው የተለያዩ መረጃዎችን በመንዛት ህብረተሰቡን በተለይ ወጣቱን ለሁከትና ነውጥ ለማነሳሳት የሚያደርጉትን ሩጫ ማጋለጥ የሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ ሃላፊነት ሊሆን ይገባል። የነውጥ ሃይሎች የጥፋት ተልኳቸውን ትኩረት አድርገው እየሰሩ ያሉት የብሄር ግጭቶች እንዲፈጠሩና እንዲስፋፉ ማድረግ ላይ ነው። የጥበትና ትምክህት ሃይሎች ዓላማቸውን ለማሳካት ሁሌም ነውጥና ሁከትን ይመርጣሉ። ነውጥና ሁከት መፍጠርና በተለይ በብሄሮች መካከል የሚደረግ ግጭት የጥፋት ሃይሎች ዋንኛ ስትራቴጂያቸው ነው።
ግምገማ የኢህአዴግ የጥንካሬ መሰረት ነው፡፡ ኢህአዴግን ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ እስከ አገርና ህዝብ መምራት ደረጃ ውጤታማ እንዲሆን ካደረጉት አበይት ምክንያቶች ውስጥ አንዱና ቀዳሚው ይህ ጠንካራ የግምገማ ባህሉ እንደሆነ በርካቶች ይስማማሉ፡፡ ይህ የግምገማ ባህሉ አባላቱ ጥሩ የስነ ምግባር ምንጭ እንደሆናቸው፣ ተጠያቂነትን እንዲያውቁና የተጣለባቸው ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ካደረጋቸው ምክንያቶች ቀዳሚውና ዋነኛው ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ አሁን ላይ እነዚህ የኢህአዴግ ጠንካራ መሰረት እየተሸረሸሩ እንደመጡ አንዳንድ ሁኔታዎች ያመላክታሉ። ይሁንና ከድርጅቱ የቆየ ልምድ ኢህአዴግ ወደ ቀድሞው አቋሙ ለመመለስ የሚከብደው አይመስለኝም። ኢህአዴግ በቡድን አሰራር ላይ መሰረት ያደረገ ፓርቲ በመሆኑ አንዳንድ ግለሰቦች ቢበላሹም ድርጅቱ ላይ የሚከሰተው ተጽዕኖ እጅግም ነው። ለዚህ ነው ኢህአዴግ ወደ ቀድሞው አቋሙ ለመመለስ አይከብደውም ለማለት የደፈርኩት። በኢህአዴግ ቤት ማንም በዛሬ አቅሙ እንጂ በትናንት ማንነቱ የማይለካው።
ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት በእያንዷንዷ የአገራችን ስኬት ላይ የኢህአዴግ ጉልህ አሻራ አርፎበታል። አገራችን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የተመሰከረላት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለተከታታይ 15 ዓመታት በማስመዝገብ የዜጎች ህይወት መለወጥ ኢህአዴግ ከፍተኛ ድርሻ አለው፤ በአገራችን የህዝብን አንገት አስደፍቶ የነበረውን ድህነትን ከግማሽ በላይ እንዲቀንስ አድርጓል። በጦርነት ትታወቅ የነበረች አገር ዛሬ አስተማማኝ ሰላም ማረጋገጥ በመቻሏ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለመሆን በቅታለች፤ በስንዴ ልመና ትታወቅ የነበረች አገር ዛሬ ላይ በምግብ ሰብል ራሷን ችላለች፡፡ እጅግ ከባድ የተባለውን ከ2008 ጀምሮ ተጽዕኖው እስካሁን የዘለቀውን ድርቅ በአመዛኙ በራሷ አቅም መወጣት ችላለች።
አገራችን በምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ የዲፕሎማሲ የበላይነት እንዲኖራት በማድረግ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዓቀፍ መድረኮች ተሰሚነት እንዲኖራት ኢህአዴግ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎችን አከናውኗል። ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ በአካባቢያዊም ሆነ አህጉራዊ እንዲሁም በዓለም ዓቀፋዊ መድረኮች ያላት ተሰሚነት እጅጉን አድጓል። በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እንድትታወቅና አዲስ ገጽታ እንድትላበስ ኢህአዴግ የአንበሳውን ድርሻ አበርክቷል፤ በማበርከትም ላይ ይገኛል። እነዚህ ሁሉ ስኬቶች የኢህአዴግ አይደሉምን?
ባለፉት 23 ዓመታት ኢትዮጵያ ህገመንግስ ታዊና ጠንካራ አገር ለመሆን የበቃችው፤ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ነጻነትና እኩልነት የተረጋገጠው፣ ጅምር ቢሆንም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መለማመድ የጀመርነው፣ በተከታታይ ለ15 ዓመታት ባለሁለት አሃዝ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማስመዝገብ ሁሉም በየደረጃው ፍትሃዊ ተጠቃሚ መሆን የጀመረበት፤ ድህነት እንዲቀንስ የተደረገው፤ የአገራችን ተሰሚነት በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እጅጉን ከፍ ያለው፤ አገራችን በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚም በአፍሪካ ትኩረት የምትስብ አገር ለመሆን የበቃችው በኢህአዴግ አመራር ነው።
ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ የምናስተውላቸው አንዳንድ ነገሮች ግን የኢህአዴግ ባህሪያትና ባህሎች አይደሉም። ኢህአዴግ ከቀድሞው አቋሙ እየተንሸራተተ ነው፤ ዛሬ በኢህአዴግ ቤት ህዝበኝነት እየገነገነ መጥቷል፤ ሁሉም በየቅሉ መጓዝን መርጧል። በዚህ አካሄድ የህዝብ ተጠቃሚነት አይረጋገጥም፤ የአገር አንድነት፤ የህዝቦች አብሮነት አይጠበቅም። ህዝበኝነት የህዝብን ስሜት በመኮርኮር የህዝቦችን አብሮነት ይሸረሽራል፤ ህዝብን ያባላል፤ አገርን ይበትናል። በመሆኑም ኢህአዴግ ውስጣዊ ችግሩን ለማስወገድ፣ በፍጥነት ወደ ቀድሞ አቋሙ ሊመለስ ይገባል። ሰሞኑን የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እያደረገ ባለው ስብሰባ የእያንዳንዳችንን ህይወት የሚመለከት በመሆኑ የኢህአዴግ አመራሮች ሆይ ለህዝባችሁ፣ ለአገራችሁ እንዲሁም ለራሳችሁ ስትሉ ቆም ብላችሁ ሁኔታዎችን መርምሩ፤ ተቀጽላውን ቆርጣችሁ ጣሉ።

አባ መላኩ

Published in አጀንዳ

በአሁኑ ወቅት ሱስም እንደፋሽን ተከታዩ በዝቷል። የአንዱ ቀዳዳ ሲዘጋ ሌላው እየተከፈተ፤ ቁጥጥሩ ጠንከር ሲል ሌላ መንገድ እየተቀየሰ፤ ወጣቱ እንደቀልድ ለሙከራ በጀመረው ስህተት እየተጠለፈ፤ በሱስ ሰንሰለት ታስሮ መውጫ ቀዳዳ አጥቶ ሲማስን ይታያል።
መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት በወጣቶች ላይ የተጋረጡትን ችግሮች የመቀነስና የወጣቶችን ሰብዕና ለመገንባት የተለያዩ ተግባራትን እንደሚያከናውን ይታወቃል። ይሁን እንጂ ሥራው በቅንጅት ባለመሰራቱ የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ ሲሆን አይታይም።
የተለያዩ የአደንዛዥ እፅ መሸጫዎችና መጠቀሚያዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፉ መምጣታቸው ደግሞ የመከላከል ስራው ውጤታማ አለመሆኑን ያሳብቃል። የአደንዛዥ እፆቹ እየተስፋፉ የሚገኙት ደግሞ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አልፈው በመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አቅራቢያ መሆኑ ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል።
በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አቅራቢያ ያሉ የንግድ ቤቶች በሱስ የተጠመዱ ተማሪዎች መደበቂያ መሆናቸው ይፋ ተደርጎ እንደነበር አይዘነጋም። የሱስ ማዘውተሪያ ቤቶቹ በዋነኛነት በሱቆች፣ በፊልም ማከራያዎች፣ በጸጉር ቤቶችና በጀበና ቡና እንዲሁም በተለያዩ ንግድ ቤቶች ሽፋን አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው። በእነዚህ ቤቶች የሚገለገሉ ተማሪዎች ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተጠቅሶ ተዘግቦ ነበር።
አሁን አሁን ደግሞ በይፋ ከሚታወቁት አደንዛዥ እፆች በተጨማሪ ለህመምተኞች የሚታዘዙ መድሃኒቶችን በመጠቀም ተማሪዎች ራሳቸውን እያደነዘዙ፤ ለከፋ የጤና ቀውስ እየተጋለጡ እንደሚገኙ መረጃዎች እየወጡ ነው። በተለይም የችግሩን ስፋት የሚያሳየው ድብርትን ለማስወገድ ወይም ለመነቃቃት ተብለው በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚገኙ የመድሃኒት መደብሮች ካለሃኪም ማዘዣ የሚቸበቸቡት መድሃኒቶች ተጠቃሽ ናቸው።
በመሆኑም አደንዛዥ እፆችና የወጣቶችን ሰብዕና በተበላሸ መልኩ የሚቀርጹ ሁኔታዎችና ተፅዕኗቸውን ማህበረሰቡ እንዲገነዘብ ማድረግ ያስፈልጋል። ማህበረሰቡም የእያንዳንዱ ወጣት ሰብዕና መበረዝና ሱስ ውስጥ መዘፈቅ ለአገር የሚያመጣው መዘዝ እጅግ ከፍተኛ መሆኑንና ለራሳቸው ለወጣቶቹም ቢሆን ከጉዳት በስተቀር ጥቅም እንደሌለው በትክክል መገንዘብና ማስገንዘብ ይጠበቅባቸዋል።
የወጣቶችን በመጤ ጎጂ ባህሎችና የአደንዛዥ እፅ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያስችል የአምስት ዓመት ስትራቴጂ እቅድ ማዘጋጀቱ አይዘነጋም። በአገሪቱ የተገነቡ የመዝናኛ ማዕከላት በቂ ካለመሆናቸው ባለፈ የተገነቡትም የሚሰጡት አገልግሎት በቂ አለመሆኑ ወጣቶችን ለሱስ ተጋላጭ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል። ይህን ችግር ያቃልላል የተባለው ስትራቴጂክ እቅድ መዘጋጀቱ ምን ውጤት እያመጣ እንደሆነ መገምገም ይገባል።
የሰብዕና ግንባታ ሥራው ወጣቶች በብዛት ከሚውሉበትና ጊዜያቸውን ከሚያሳልፉበት አካባቢ አኳያ የሚመጥን ሥራ እንዳልተሰራ ይታመናል። የወጣት ሰብዕና ግንባታ ሥራ ሲታቀድ ሱስ ውስጥ የገቡ ወጣቶችን ከሱስ ለማውጣት ብቻ መሆን የለበትም። ወጣቶች ወደሱስ ለመግባት ዕድሉ የተመቻቸ በመሆኑ አዳዲስ ሱስ ውስጥ የሚገቡ ወጣቶችንም ለመታደግ እቅድ ሊኖር ይገባል፡፡ ሁሌም ከችግር በኋላ መፍትሄ ሳይሆን አስቀድሞ የችግሩን መንስኤ በመግታት ወጣቶችን የመታደጉ ሥራ በይበልጥ ሊጠናክር የግድ ይላል፡፡
ህብረተሰቡ፣ ሱስ ህመም መሆኑንና በህክምና እንደሚድን ግንዛቤው አነስተኛ ነው፡፡ በመሆኑ ወጣቶች ሱስ ውስጥ ከተዘፈቁ በኋላ ማከም እንደሚቻል የማስገንዘብና ለሱስ እንዳይጋለጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል። ወጣቶች በብዛት የሚገኙባቸውና ለሱስ ተጋላጭ የሚያደርጉ ሁኔታዎችን ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት የትምህርት ተቋማት አካባቢ የሚስፋፉ ለሱስ አጋላጭ ንግዶችን ለማስወገድ በቅንጅት መስራት ይገባል፡፡
ነገ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለሚያስፈልጋት አገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ከሱስ የጸዳና ባለ ብሩህ አዕምሮ ተማሪዎች ያስፈልጉታልና ሁሉም ከወዲሁ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት አለበት። በለሱን የጠበቀ ብቻ ነው ፍሬዋን ሊበላ የሚችለው፡፡ ካልሆነ ግን ዛሬ በአግባቡ ያልጠበቅናቸውና ያልተንከባከብናቸው ወጣቶችና ታዳጊዎች ነገ የአገር ስጋት መሆናቸው አይቀርም፡፡
የወደፊት የአገር ተረካቢዎች በሱስ እንዲጠመዱና ከመንገዳቸው እንዲሰናከሉ ምክንያት የሚሆኑ የንግድ ተቋማትም ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል፡፡ የሚመለከተው አካል በቃችሁ ሊላቸው ይገባል፡፡ ትምህርት ቤቶችም የቀለም ትምህርትን ከመስጠት ባለፈ በስነምግባር የታነጹ ዜጎችን የማፍራት ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ በለሶቻችን ተንከባክበን በማሳደግ የነገ አገር ተረካቢዎችን ስብእና መገንባት የሁላችንም ኃላፊነት መሆን ይኖርበታል፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

አዲስ አበባ፡- ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በኢትዮጵያ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ ካልተሠራባቸው በቀጣይ ትልቅ ስጋት በመሆን የህብረተሰቡን ጤና አደጋ ላይ ሊጥሉ እንደሚችሉ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃን ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ጤና አጣባበቅ ማህበር 29ኛ ጉባኤውን በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የስብሰባ አዳራሽ ባካሄደበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመሩ መጥተዋል፡፡ አገሪቱ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት በስኳር ህመም ታማሚዎች የመሪነቱን ቦታ መያዟም ችግሩ ምን ያህል አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚጠቁም ነው፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ በአገሪቱ በተለይም የስኳርና የኩላሊት በሽታዎችና እፅ ከመጠቀም ጋር ተያይዞ የሚመጡ የአዕምሮ ህመሞች በከፍተኛ ደረጃ እየጨመሩ መጥተዋል፡፡ ጤናማ የአመጋገብ ስርዓትን አለመከተል፣ በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግና አልኮልና ሌሎች ሱስ አምጪ እፆችን መጠቀም የችግሩ ዋነኛ መንስኤዎች ናቸው፡፡
ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ለህብረተሰብ አደጋ እየሆኑ የመጡትን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በተመለከተ ለመከላከል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ደንብ በማዘጋጀት የተደራጀ የህብረተሰብ ጤና አደጋ አገልግሎት እንዲቋቋም ያደርጋል፡፡ የተደራጀ የሰው ኃይልና የተደራጀ ሀብት በመመደብም የሚሠራ ይሆናል፡፡ ህብረተሰቡ ጤናማ የአመጋገብ ስርዓት እንዲኖረውና በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ትምህርት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ይህን ማድረግ የማይቻል ከሆነም በተላላፊ በሽታዎች ምክንያት የህዝቡን ጤና ማከም በማይቻልበት አደጋ ውስጥ ይወድቃል፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።