Items filtered by date: Friday, 02 March 2018

በዘመነ መሣፍንት ማዕከላዊ መንግሥት ተዳክሞ አካባቢያዊ ገዥዎች ለስልጣን ይታገሉ ነበር። ለማያቋርጥ እልቂትም ምክንያት የሆኑ ጦርነቶች ለአገርና ህዝብ የማይመቹ ነበሩ። ይሁን እንጂ ከብዙ ጊዜ በኋላ ማዕከላዊ መንግሥት በድጋሚ ተጠናከረ። ከዚሁ ጋርም በመጀመሪያ አካባቢ አገራዊ ነፃነትና ክብርን ለማስጠበቅ የሚረዳ የብዝሃነት መንፈስ ነበር። የአገሬው ሕዝብ ለማዕከላዊው መንግሥት እውቅና ሰጥተው ከራሳቸው ጎሳ በወጡ ገዢዎች እንዲተዳደሩ የሚፈቅድ ዓይነት ባህሪ ነበረው። አፄ ምኒልክ የሚመሩት ማዕከላዊ መንግሥት ለጦርነቱ የክተት አዋጅ ሲያወጣ ለጋራ አገራቸው ቀናዒ የነበሩ ህዝቦች ለነፃነታቸው ጥሪውን ተቀብለዋል፤ በሙሉ ልብም ዓድዋ ላይ ዘምተዋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ዓድዋ ወረዳ የሚገኝ በተራራ የተከበበ ሰፊ ሜዳ ላይ፤ ጦርና ጋሻ አንካሴና ጎራዴ ጠብመንጃና ሰነኔ የያዙ፤ ብልኮና ነጠላ፣ በርኖስና ካባ የደረቡ በባዶ እግራቸው የሚሄዱ ተሰልፈዋል፡፡ በሌላ በኩል ይህንን ብዙ ሺ ወታደሮች መድፍና መትረየስ ቦምብና ዘመናዊ ጠብመንጃ ሽጉጥ፣ ሳንጃና ሴንጢ ታጥቀው በጥይት ሊቆሏቸው ቆብና ኮፊያቸውን ደፍተው ተደርድረውና መሽገው ቆመዋል፡፡ ጦርነቱ ሲጀመር የሸዋ ፈረሰኛ፣ የጎጃም እግረኛ የትግራይ ነፍጠኛ የአማራ ሰልፈኛ የደቡብና የኦሮሚያ ተዋጊዎች ወኔና ጀግንነት ያንን ያናፋውን ጠላት ይቆላውና ያንገዳግደው ጀመር፡፡ ጥቂት ቆይተው ሜዳው ደም ለብሶ፤ ሳሩና አፈሩ ቀይ ሆነ፡፡ ጥቁሩም ነጩም ወንድ ልጅ ተናንቆ አንደኛው ባሪያ የሚያደርገው ፍለጋ ሌላው ለመብቱ ተያይዘው ወድቀዋል፡፡ ጉዳት የደረሰበት ተጋድሞ ያቃስታል፡፡
ጦርነቱ የፈጀው ጥቂት ሠዓታት ብቻ ነበር፡፡ በዚህም ኢትዮጵያዊያን በጀግንነት በከፈሉት መስዋዕትነት በሺዎች የሚቆጠሩ ኢጣሊያውያን ሞተውና ቆስለው፤ የተቀሩት ደግሞ ተማረኩ። ሸሽተው ያመለጡ ወታደሮች ቢኖሩም ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የጣሊያን የጦር መሳሪያ በኢትዮጵ ያውያን ተማረከ።
ወቅቱ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ጥቁሮችና ጭቁን ህዝቦች በነጮች የበላይነት በቅኝ ግዛት የሚማቅቁበት ነበር። የዓድዋ ድል በነጮችና በ‹‹ኢምፔሪያሊዝም›› ላይ የተገኘ የመጀመሪያው ግዙፍ ድል ሆነ በዓለም ታሪክም ተመዘገበ።
ድሉ የኢትዮጵያ ልዩ ህብረት፤ የአንድነትና የሰንደቅ ዓለማችን ክብር ጎልቶ የታየበት ነው፡፡ የበርካታ አባቶቻችንና እናቶቻችን አጥንት የተከሰከሰበት፣ ክቡር የነጻነትና የህይወት ዋጋ ነው፡፡ ለዚህም ነው እጅጋየሁ ሽባባው /ጂጂ/ እንዲህ ያንጎራጎረችለት፡፡
የተሰጠኝ ህይወት ዛሬ በነጻነት፣
ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት፤
ስንት ወገን ወደቀ በነጻነት ምድር፤
ትናገር ዓደዋ ትናገር አገሬ፤
እንዴት እንደቆመች ከፊታችሁ ዛሬ ፤
ድል አምባ ዓድዋ አፍሪካ እምዬ፤
ኢትዮጵያ!...
ታላቁን የስቃይ እና የደስታ ቀንን ያስተናገደችው ዓድዋ፤ የሰው ልጆች እኩልነትን የድል መንሳት ቁልፉ ቀለም አልያም ስልጣኔ ሳይሆን ጀግንነት መሆኑ ለዓለም ተመሰከረላት፡፡ አውድማዋ ዓድዋ! ለመላው ጥቁር የኩራት፤ ለነጩ የሀፍረት ካባን ያጎናፀፈች ዓድዋ!
እድልም አጋጣሚም ሆኖ በተሰጠን ሁሉ ይህን ቀን መዘከርና ትላልቅ አስተሳሰቦችን አብሮ እያጠኑና እኩል እየተከፋፈሉ መኖር የወሰንን ሰዎች ምንኛ እድለኛ እንደሆንን መግለጹ ከቃል በላይ ነው፡፡
ይህች ቀን ሕያው ሆና የምትቆይ የኢትዮጵ ያዊነት ትስስር ናት፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ትስስርና ፍቅር ደግሞ በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ አንዴ ወይም ሁለቴ የሚመጣ ነው። የነጻነትና የባርነትን አንድምታ ሰሙና ወርቁን ፈልፍሎ በማውጣት እንቆቅልሹን እንድንፈታ ያደረግነው በዛሬዋ የድል ቀን ነው፡፡ ታላላቅ የሰው ልጆች ለዘመናት ከሰበሰቡትና ካጠራቀሙት ኮትኩተውም ጠብቀውም ለትውልዱ ካሳለፉት ባህልና ተመክሮ ሞራልና እሴቶች የተስተካከለ ኑሮ ለመኖር አውጥተው አውርደው ከአስቀመጡልን የድል ጎተራ የተገኘች ናት፡፡
ለጥቂት ሰዓታትና ደቂቃ እንዲሁም ሴኮንዶች በአይነ ህሊናችን ቃኝተን ጥልቁ የአንድነት ትርጉም በታየበት እዚያች ተራራ ላይ ብንከትም ያልተገለጡልን እልፍ መስዋእትነቶች ይታዩናል፡፡
ለዚህች አገር ውለታን የዋሉ ጀግኖቻችን ያኔ በሰማዕትነት ደማቸው ፈስሶ፤ አሁን በድህነት ቤታቸው ፈርሶ በዓመት አንዴ ብቻ በስማቸው ሻማ እየተለኮሰ ይዘከራሉ፡፡ እንደ እኔ ግላዊ ምልከታ ይህ ትውልድ የአባቶቹን ታሪክ መድገም ይቅርና ማወቅም መናፈቅም የሚፈልግ አይመስልም፡፡ ይልቁንም አሁን ላለበት ችግሩ የቀደሙትን እንዲወቅስ ሆኖ ተቃኝቷል፡፡
አንድ በባህር ማዶ ኑሮ ፍቅር ያበደ ብልጭልጭ የወንዜ ልጅ ‹‹ምናለ በጣልያን በተገዛን ኖሮ!›› ብሎ በብርቱ ሲያማርር ሰማሁት፡፡ ከራስ ፀጉሩ እስከ እግር ጫማው ድረስ አለባበሱ በአንገቱ፣ በእጁና በእግሩ ላይ የከመረው የቅራቅንቦ መዓት፤ ሱሪውን ዝቅ አድርጎ ግልገል ሱሪውን እያሳየ የማያምር አማርኛን ከተሰባበረ እንግሊዘኛ ጋር እየቀላቀለ የሚያወራ ብልሹ ወጣት ስለ መገዛት ማውራቱ ይገርመኛል፡፡ የመከራ ቀንበርን መሸከም ቀረበት እንጂ እራሱን በፍቃዱ ከሸጠማ ቆይቷል፡፡ እንዲህ አይነቱ ግን ናፋቂ ተብሎ አይሰደብም፡፡ ለምን አትበሉኝ እንጂ ካላችሁኝማ ማየት የፈለገው ወደ ውጭ እንጂ ወደራሱ አይደለምና ነው፡፡
የሚገርመኝ የጣልያን ወጣቶች የኛን ዓርበኞች ለመጎብኘትና አልፎ ተርፎም ሊረዷቸው እየተንከባከቡም በክብር ሊያኖሯቸው ወደ አገራችን ይመጣሉ፡፡ ያኛው ብልጭልጭ ናፋቂው ወጣት ደግሞ በሀሳብ ይሰደዳል፡፡ ምናልባት ወደ አባቶቼ ብመለከት ናፋቂ እባል ይሆን ብሎ ሰግቶ ይሆን? እንጃ ብቻ አሁንም እዚያው ነው፡፡
የጀግኖች አባቶቻችንን ታሪክ ለመዘከር ከተለያዩ ከተማዎች የተውጣጡ ታሪክ የሚሰሩ ጥቂት ብርቱ ወጣቶች ከመዲናይቱ አዲስ አበባ እስከ ዓድዋ ተራሮች ድረስ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን ለበርካታ ቀናት ያህል እጅግ በጣም አድካሚና ፈታኝ በሆነ የጸሃይ ንዳድ እየተፈተኑ በእግር ሲጓዙ የበርካቶች ሀሳብም ተከትሏቸዋል፡፡ በተቃራኒው እቤቱ ሆኖ በቅዠት ዓለም አውሮፓና አሜሪካን በሀሳቡ የሚዳክርም እልፍ ነው፡፡
ለብዙ ዓመታት ከድሉ ታሪክና ፋይዳ ይልቅ በሰፊው የሚታወቀው የድምፃዊት እጅጋየሁ ሽባባው /ጂጂ/ ‹‹ትናገር ዓድዋ›› የሚለው ሙዚቃ ነበር፡፡ እውነት ለመናገር እሷ ምስል ከሳች በሆነ ግሩም ግጥምና ጆሮ ገብ በሆነ ውብ ዜማ ጥሩ አድርጋ ባትዘፍንልን እንዲሁም ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎቻችን በዓመት ለአንድ ጊዜ ብቻ ባያጫውቱት ኖሮ ምን ይውጠን ነበር? ምናልባት ውድ እና ብርቅዬ አርበኞቻችንን ከየወደቁበት አሰባስቦ በማምጣት ምኒልክ አደባባይ ጋ ቪዲዮ ቀርፆ ዜና ከማንበብ በዘለለ ማለቴ ነው፡፡ አሁን ግን እድሜ ለሙዚቀኞቻችን ተጨማሪ ሙዚቃዎችን ስለመረቁልን ዘፈኖቹ ቁጥራቸው አድጎ በህሊናችን የሳልነውን አሰቃቂውን የጦርነት አውድማ በቪዲዮ መልክም ተቀንጭቦ ለማየት በቅተናል፡፡
ዛሬ ላይ እንደ ዓድዋ ከመሳሰሉ ታላላቅ ድሎች ይልቅ ለኳስ ድል በደስታ እየተዘፈነ በሀሴት ይፈነደቃል፡፡ አሁንማ ለቢራም ለታሸገ ውሃም ኧረ እንዲያውም ለ‹‹ሊፒስቲክም›› ይዘፈናል፡፡ ጉድ እኮ ነው እናንተ! ጀግኖቻችንን የማወደስ እና የመዘከር ባህላችን ሲበዛ ከሲታ ነው፡፡ በዓድዋ ጦርነት ከጠላት ጋር ለመፋለም ያገለገሉ የጦር መሳሪያዎች የትም ወድቀውና በስብሰው በቅርብ ዓመታት ለጦርነት የዋሉ መሳሪያዎች በክብር ነግሰው የተቀመጡባቸው ሙዚየሞቻችን ስንት ናቸው? አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህንፃዎቹን በብሔራዊ ጀግኖቻችን መታሰቢያ ከመሰየም ይልቅ ሲሻው ‹‹ኬኔዲ›› ሲሻው ‹‹ማንዴላ›› ይላቸዋል፡፡ አሁን ከሚገነቡት ሁለት ትልልቅ ህንፃዎች መካከል የአንዱ ስም ኦባማ ሊባል እንደሚችል በግቢው እየተወራ ነው፡፡ በጀግኖቻችን ስም መታሰቢያ ሕንፃ ባንገነባ እንኳ ታላላቅ ጀግኖቻችንን የምናስታውስበትን ታሪካዊ ቤታቸውን ባለማፍረስ መታሰቢያነቱን ብንጠብቅ ምናለበት?
ላለፉት በርካታ ዓመታት የዓድዋ ድል ለተማሪና መንግሥት ሰራተኞች የዕረፍት ጊዜ፤ ለአንዳንዶች የትርፍ ሰዓት ሥራ ተጨማሪ ገቢ ከመሆን የዘለለ ብዙም ትርጉም አልነበረውም፡፡ አሁን ግን ከመቼውም ግዜ የበለጠ የመነቃቃት መንፈስ እያበበ ይገኛል፡፡ ለታሪካዊ ሰዎችና ቦታዎች ተገቢውን ክብር እና ዋጋ መክፈል እየተጀመረ ነው፡፡ እንደ መቅደላ አምባ ባሉ ታሪካዊ ቦታዎች ላይ ምንም እንኳን አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በበቂ ሁኔታ ባይኖሩም ዩኒቨርሲቲ ተከፍቷል አንዳንዴም ከላይ መጀመር ጥሩ ነው፡፡
ሲጥር የወደቀ ከአሸናፊዎች እንደ አንዱ ነው እንደሚባለው፡፡ ሰው መሆን በህይወት ስንክሳሮች ተፈትኖ የማለፍ ውጤት ነውና፡፡ ታሪካችንን ለመዘከርና ለማወቅ የጣርነውን ያህል በመሆኑ በዚህች ዓለም ያለ መስዋዕትነት እክል እንጂ ድል የለም፡፡ የኑሮን ወለል ለመጨበጥ የህይወትን ትግል በድል መወጣት ተገቢ ነው፡፡ ህይወታችንን ከወትሮአችን የተሻለች ለማድረግ አልባሳታችንን ብቻ ሳይሆን ታሪክ የማወቅ አእምሮአችንንም የማስቆንጀት ሥራ መስራት አለብን፡፡ ልክ እንደ ጀግኖች አባቶቻችን፡፡ ታሪክ መስራት ራስን ከመግራት ይጀምራል፡፡ ያሉንን ስናውቅ የጎደለንን እንተካለን፡፡ የእውቀቶች ሁሉ ታላቅ እውቀት ያለንን ታሪክ በመረዳት ራሳችንን ሆነን መኖር መቻል ነው፡፡ የህይወት ርምጃችን ራሳችንን ከማወቅ ስንጀምር መመንመን ሳይሆን መለምለም እንጀምራለን፡፡
ብንበላበት ለሚጣፍጥ ብንለብስበትና ብናጌጥበት ለሚያምርብን የድል ታሪክ ጊዜን ሰጥቶ ማውሳት የግድ ነው፡፡ ትክክለኛው የአእምሮ እርካታ ያለው የራስ በሆነ የነጻነት አገር ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ከሰው ዶሮ የራስ ሽሮ እጅጉን ያጠግባል፡፡ ከሰው ህንጻም የራስ ደሳሳ ጎጆ ታስከብራለች፡፡ ከባርነትም ነጻነት እጅጉን ጠቃሚ ናት፡፡

አዲሱ ገረመው

 

Published in ስፖርት
Friday, 02 March 2018 21:42

ታሪክ ሲመዘዝ

በተለምዶ አሮጌ ቄራ እየተባለ በሚጠራው ወይም በቤተመንግሥት አካባቢ ዕድሜ ጠገብ የሆኑ መኖሪያ መንደሮች እንደነበሩ ትዝታው ገና ከአዕምሮአችን አልጠፋም፡፡ መንደሮቹ ከዕድሜ ብዛት በጣም ያረጁ በመሆናቸው ለመኖሪያ ምቹ አልነበሩም፡፡ መንደሮቹ ለመልሶ ማልማት በቅርቡ ፈርሰዋል፡፡ ከእነዚህ ዕድሜ ጠገብ መኖሪያ ቤቶች መካከል በአሠራሩ ለየት ያለ፣ እንደ እድሜ ጠገብነቱ ያልተጎሳቆለ፣ ጎልቶ የሚታይ ቢሆንም ታሪኩ የተደበቀ ባለአንድ ፎቅ መኖሪያ ቤት ይገኛል፡፡ በዙሪያው የነበሩት መንደሮች ሲፈርሱ ይህ ቤት አልፈረሰም፡፡ በአካባቢው ካሉ ጥቂት የቀሩ ቤቶች ከፍ ብሎ ከሩቅ ይታያል፡፡ ብቻውን መቅረቱ የበለጠ እይታ ውስጥ እንዲገባም አድርጎታል፡፡
ማገሩና ቋሚው በወይራ ጥርብ እንጨት የቆመው ይህ ቤት ግድግዳው የጭቃ ልስን ነው፡፡ ባለአንድ ፎቅ ሲሆን፣ የፎቁ መወጣጫና መሬቱ በሳንቃ የተሠራ ነው፡፡ 15 ክፍሎች አሉት፡፡ የቤቱ መስኮቶች በአራቱም ማዕዘናት አዲስ አበባን ለማየት እንዲያስችሉ ተደርገው የተሠሩ ናቸው፡፡ በፎቁ በረንዳ ላይ ሆነውም አዲስ አበባን በአራቱም አቅጣጫ ይቃኛሉ፡፡ ድንገት የመጣ ጠላት ማምለጫ የለውም፡፡ በቀላሉ በእይታ ውስጥ ይገባል፡፡ «ስትራቴጅ ቦታ» እንደሚባለው ማለት ነው፡፡
በቤቶቹ በሮች ላይ የሚታየው የተለያየ የቅርፅ ሥራ እንኳን አልደበዘዘም፡፡ የቤቱ ጣሪያ የተሠራበት እንጨትም ዕድሜ አላጎሳቆለውም፤ ብል አልበላውም፡፡ በቤቱ ውስጥ ያሉት የእንጨት መገልገያዎች ዕድሜ ጠገብነታቸውን ከማሳበቃቸው በስተቀር ከዚህ በኋላም ረጅም ጊዜ የሚያገለግሉ ሆነው ነው ያገኘኋቸው፡፡ ከብረት፣ ከኒኬልና ከነሐስ የተሠሩት የቤት ውስጥ መገልገያዎች ዝገት አልጎበኛቸውም፡፡ የመገልገያ ቁሶቹ በብዙ ሰዎች እጅ አልፈው አለመጎሳቆላቸው ደግሞ ይበልጥ ያስገርማል፡፡ በተለያየ መጠን የተሠሩት የሸክላ ውጤቶች እንስራና ገንቦ ዘመን አይሽሬነታቸውን አስመስክረዋል፡፡ በቤት ውስጥ ያየኋቸው ሁሉ የሚያስደምሙ የታሪክ አሻራ ያረፈባቸው ናቸው፡፡ በዛን ዘመን የተነሱት ፎቶግራፎች እንኳን አልወየቡም፡፡
ቤቱ የተገነባበት ዘመን በግምት ካልሆነ በትክክል አይታወቅም፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ መቆርቆር ጋር እኩል የሆነ ዘመን እንዳለው ግን ይገመታል፡፡ ባለአንድ ፎቅ የሆነው ይህ ቤት በአራት መቶ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን፣ በቅርሶቹ ላይ የግሪኮችና የህንዶች የእጅ ሥራ እንዳረፈበት ይገመታል፡፡ ቤቱ ትውልድ ተቀባብሎት ጉዳት ሳይደርስበት በአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በቅርስነት ተመዝግቧል፡፡ በከተማዋ ማስተር ፕላን ውስጥ ተካትቶ ለትውልድ እንዲሸጋገር መደረጉ ለታሪክ የተሰጠውን ትኩረት ያሳያል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ትልቅ ስምና ታሪክ ያላቸው የብዙ ሰዎች መኖሪያ ቤቶች ፈርሰዋል፡፡ ይህ ቤት ግን ተርፎ ዛሬ እኛም ስለቤቱና ስለቤቱ ባለቤት ለማውሳት በቅተናል፡፡ የቤቱ ባለቤት ወይዘሮ ይምጡበዝና ሀብቴ መሆናቸው ደግሞ ታሪኩን ይበልጥ ያጎላዋል፡፡ የእኝህ ሴት አራተኛ ትውልድ የሆኑት አቶ ብርሃኑ መንግሥቱ እንደነገሩን ቤቱ በቤተመንግሥት አካባቢ እንዲሠራ የተደረገው ወይዘሮ ይምጡበዝና የቤተመንግሥት ዙፋን ችሎት ታዛቢ ሆነው ያገለግሉ ስለነበርና በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ከጦር መሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት ባለቤታቸው ቢትወደድ ወልደ ገብርኤል ለቤተ መንግሥት በነበራቸው ቅርበት ጭምር ነው፡፡
ቤቱ ከመሠራቱ በፊት ወይዘሮ ይምጡበዝና ከተክለሃይማኖት አካባቢ በፈረስ እየተመላለሱ ነበር በቤተመንግሥት ውስጥ የችሎት ሥራቸውን የሚሠሩት፡፡ የአሮጌ ቄራ ወንዝንም በወቅቱ በፈረስ ነበር የሚሻገሩት፡፡
አቶ ብርሃኑ ሲነገር እንደሰሙት ወይዘሮ ይምጡበዝና ትውልዳቸው መንዝ ነው፡፡ ከአፄ ምኒልክ ጋርም የቀረበ ዝምድና አላቸው፡፡ ወደአዲስ አበባ ከተማ ለመምጣትም ምክንያት የሆናቸው ቤተሰባዊ ትስስሩና የተሰጣቸው የሥራ ኃላፊነት ነው፡፡ ታሪካቸው እንደሚያስረዳው ፍርድ አዋቂነታቸው፣ ብልህ ሴት መሆናቸውና ሩህሩህ እንደነበሩም ይነገርላቸዋል፡፡ ወይዘሮ ይምጡበዝና የወለዱት አንድ ሴት ልጅ ነው፡፡እርሳቸውም ወይዘሮ ሙላተወርቅ ይባላሉ፡፡ ወንድማቸውም ሽመልስ ሀብቴ ይባላሉ። አርበኛ ናቸው፡፡ ሽመልስ ሀብቴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በሚል በስማቸው ትምህርት ቤት ተሰይሟል፡፡ ወይዘሮ ይምጡበዝና በ1940ዎቹ አካባቢ እንዳረፉ ይነገራል፡፡
አቶ ብርሃኑ እንደገለፁልን ጥንታዊ ቤቶችን የሚያጠኑ የውጭ አጥኚዎች በተደጋጋሚ ቤቱን ጎብኝተዋል፡፡ ጥናትም አካሂደዋል፡፡ ቤተሰቡ ቤቱን ጠብቆ ከማቆየትና በተባራሪ ከሰማው ታሪክ ባለፈ የወይዘሮ ይምጡበዝናን የተሟላ ታሪክ ማግኘት ባለመቻሉ በተደራጀ ሁኔታ በሰነድ ለማስቀመጥ አልቻለም፡፡ በሁለት ኢጣሊያናውያን ፀሐፍት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ስለሚገኙ ጥንታዊ ቤቶች የተፃፈ አንድ መፅሐፍ ማግኘታቸውንና ከጥንታዊ ቤቶቹ አንዱ የወይዘሮ ይምጡበዝና መሆኑን አቶ ብርሃኑ ነግረውናል፡፡
እንደወይዘሮ ይምጡበዝና የተደበቁ፣ ታሪካቸውም በአግባቡ ተሰንዶ ያልተቀመጠ እንዳሉ መገመት አያዳግትም፡፡ በአድዋ ጦርነት ትልቅ ገድል ያላቸው እቴጌ ጣይቱ ብጡልም ቢሆኑ ያልተዘመረላቸው እንደሆኑ ይነገራል፡፡ ከጀግኖች ወንድሞቻቸው ጋር ለሀገራቸው ጀብዱ የሠሩና ብዙ ታሪክ ያላቸው ሴቶች እያሉ ግን ታሪካቸው በአግባቡ ባለመታወቁ ሠርተው እንዳልሠሩ ሆነዋል፡፡ ትውልድም እንዳያውቃቸው ታሪካቸው በአግባቡ ባለመስፈሩ ማስተላለፍ አልተቻለም፡፡ ቢዘገይም ግን በሂደት መውጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ በተለይ እንደ እነ አቶ ብርሃኑ መንግሥቱ ለታሪክ ተቆርቋሪ የሆኑ ቢተባበሩ ብዙ ታሪክ ያላቸውን ሴቶች ማግኘት አያዳግትም፡፡ እኛም ወይዘሮ ይምጡበዝናን በአድዋ ድል በዓል ማንሳታችን ከአድዋው ድል በኋላም ቢሆን ለሀገራቸው በተለያየ የሙያ ዘርፍ የሠሩ ሴቶች መኖራቸውን እግረመንገዳችንን ለማስታወስም ጭምር ነው ታሪክን መምዘዛችን፡፡

ለምለም መንግሥቱ

Published in ማህበራዊ

« እቴጌ ጣይቱ - እቴጌ ብርሃን
ዳዊቷን ዘርግታ - ስማልኝ ስትል
ተማራኪው ጣሊያን - ውሃ ውሃ ሲል
ዳኛው ስጠው አለ - ሰላሳ በርሜል
እንደ ብልኃተኛ እናት - እንደ እመቤታችን
ሲቻለው ይምራል - የእኛማ ጌታችን »
በማለት ለአፄ ሚኒልክ የተገጠመውን ግጥም የሰሙትን ያጫወቱን የ95 ዓመቱ አባት ዓርበኛ መኮንን መሸሻ በዓድዋ የጦርነት አውደ ውጊያ ላይ ባይኖሩም አያታቸውና አባታቸው ተዋግተዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸው ለሀገራቸው የከፈሉት መስዋዕትነትና ዓድዋ ላይ የተደረገውን ተጋድሎ ታሪኩን ከአባታቸው እየሰሙ ነው ያደጉት፡፡በጦርነቱ ከሚታወሱት ጀግኖች መካከል እቴጌ ጣይቱ ብጡል አንዷ እንደሆኑና የጦር አበጋዝ እንደነበሩም በታሪክ ያውቃሉ፡፡
ታሪኩን ከመስማት ባለፈ ጦርነት የተካሄደበት ቦታ ድረስ በመሄድ ሜዳና ተራራውን፣በጦር አውድማው ከተሰለፉት ራስ ጎበና ዳጨውና ደጃዝማች ባልቻ የወደቁበትን ቦታ፣በዓድዋ አራት ተራሮች መካከል ጣሊያን በቦምብ፣በመትረየስና በመድፍ ጦርነት ሲከፍት የኢትዮጵያ ጀግና ጦር፣ ጋሻና ጎራዴ ታጥቆ እየፎከረ የጠላቱን አንገት በመቀንጠስ ድል የተቀዳጀበትን ሥፍራ በተደጋጋሚ ጎብኝተዋል፡፡የሰሙትን ታሪክ ገድሉ በተፈፀመበት ቦታ ተገኝተው ማየታቸው ትልቅ ኩራት ይሰማቸዋል፡፡በዚህ አጋጣሚ ግን ለዓድዋ ድል መገኘት ትልቅ ሥፍራ ለነበራቸው ለስመ ጥሩዋ ጀግና እቴጌ ጣይቱ ብጡል ዓድዋ ላይ ሀውልት አለመሰራቱ፣ መንገድም ሆነ ተቋማት በስማቸው አለመሰየሙ ቁጭት አሳድሮባቸዋል፡፡
አባት ዓርበኛ መኮንን የታሪኩ ተቋዳሽ መሆናቸውን እንዲህ ይናገራሉ፡፡ፋሽስት ጣሊያን ከ40ዓመት በኋላ ኢትዮጵያን ዳግም ለመውረር በመጣ ጊዜ የ15ዓመት ወጣት ነበሩ፡፡በጦርነቱ የነበረውን ተጋድሎ በደንብ ያውቃሉ፡፡አባታቸው በንብ መንጋ ምሽግ ያስለቀቁበትን ወቅትም አይረሱትም፡፡ታላቅ ወንድማቸውም ግንባር ለግንባር ከጠላት ጋር ተናንቀው ለሀገራቸው ዳር ድንበር መከበር ህይወታቸውን ሰጥተዋል፡፡ወላጅ እናታቸው ባለቤታቸው ዓርበኛ መሸሻ የሚገኙበትን እንዲመሩ በፋሽስት ጣሊያን ታዝዘው ትዛዙን ባለመቀበላቸው አስራአምስት ጅራፍ ተገርፈዋል፡፡ከዓድዋ ጦርነት ጀምሮ በአምስት ዓመቱ የዓርበኝነት ዘመን የተከፈለው መስዋዕትነት በአጭር ጊዜ ቆይታ ተነግሮ እንደማያልቅና የዓድዋ ተጋድሎም በቀላሉ የሚወሳ እንዳልሆነ ያስረዳሉ፡፡ለነፃነት ስለተከፈለው ዋጋም በግጥም እንዲህ ያወሳሉ፡፡
« ነፃነት፣ነፃነት፣ነፃነት ገዳሜ፤
እናከብርሻለን እንደ እሁድ ቅዳሜ»
አባት ዓርበኛ ወንድም ሀገሩ በዓድዋው ጦርነት ላይ አልነበሩም፡፡ዓድዋ ላይ የተደረገውን ተጋድሎና የተገኘውን ድል እንደ ማርና ወተት ታሪኩን አጣጥመውታል፡፡«የቱ ተነስቶ የቱ ይቀራል» ይላሉ፡፡ አባት ዓርበኛ ወንድም ተጨዋች ናቸው፡፡ታሪኩን እያዋዙ በወኔ ጭምር ሲነግሩን በዓድዋው ጦርነት ላይ ያሉ ያስመስላሉ፡፡«ምንም እንኳን በዓድዋ ጦርነት ላይ ባልኖርም፡፡በአያት ቅድመ አያቶቼና በወገኖቼ ድል ተደርጎ በመጣበት እግሩ ወደሀገሩ የተመለሰው ፋሽስት ጣሊያን ንቆት በነበረው ኢትዮጵያዊ በመሸነፉ ቆጭቶትና ቂም ቋጥሮ በ40ዓመቱ ሲመለስ እኔም አግኝቼው ዳግም አፍሮ እንዲመለስ በማድረጌ የታሪክ ተካፋይ ነኝ»በማለት በዓርበኝነት ዘመን የነበረውን ተጋድሎ ይገልፃሉ፡፡
አባት ዓርበኛ ወንድም በዕድሜ ቢደክሙም ወኔያቸው ገና የወጣት ያህል ነው፡፡ኢትዮጵያ በጣሊያን ቅኝ ግዛት ሥር እንዳትወድቅ፣ነፃነቷ ተጠብቆ እንዲቆይ ጀግኖች አባቶች የከፈሉት መስዋዕትነት መቼም የሚዘነጋ እንዳልሆነና ታሪኩም በወርቅ መጻፍ እንዳለበት ይናገራሉ፡፡እርሳቸው በህይወት ኖረው የሰሙትን፣ያዩትንና የተካፈሉበትን ታሪክ ለትውልድ ለመንገር መቻላቸውንም በምስጋና ይናገራሉ፡፡
በኦሮሚያ አምቦ ጀልዱ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ የዓርበኛ ቤተሰብ አቶ ነጋሳ ኡርጌሳ ስለዓድዋ ታሪክ የሰሙትንና የሚያወቁትን እንደነገሩን ጀግኖች አባቶች ለእግራቸው ጫማ ሳይሉ፣ስንቅና ትጥቅ ሳይኖራቸው፣ ዘመናዊ መሣሪያ ሳይታጠቁ፣በኃይል ሊወርር የመጣን ፋሽስት አንገት ለአንገት ተናንቀው በመዋጋት ድል እንደተቀዳጁ አባታቸው አቶ ኡርጌሳ ነግረዋቸዋል፡፡ ለድሉ መገኘት ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያውያን የነበራቸው አንድነትና የሀገር ፍቅር ስሜት ከፍተኛ እንደነበር የሰሙት ታሪክ እርሳቸው « ምነው የታሪኩ አካል ባደረገኝ» ብለው እንዲቆጩ አድርጓቸዋል፡፡
ፋሽስት ጣሊያንን ዓድዋ ላይ ድል ከነሱት ጀግኖች አባቶች መካከል አያታቸው አንዱ መሆናቸው፣ፋሽስት ጣሊያን ዳግመኛ ኢትዮጵያን ሊወርር በመጣ ጊዜም አባታቸው በተጋድሎው ውስጥ መኖራቸውና እርሳቸውም ከእነዚህ ቤተሰቦች መገኘታቸው እንደሚያስደስታቸው፤ ኩራትም እንደሚሰማቸው ገልፀዋል፡፡«ከቅኝ ግዛት ነፃ ሆና የምንኮራባትን ሀገር ላስረከቡን ጀግኖች አባቶቻችን ክብር ልንሰጥ ይገባል፡፡እኔ በህይወት እስካለሁ በቃል የማውቀውን ታሪክ ለተተኪው ትውልድ አሸጋግራለሁ»ሲሉም ታሪክን የማስተላለፍ አደራቸውን እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል፡፡
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች ዓርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ስለሺ«ዓድዋን ሳስታውስ በበለጠ በኢትዮጵያዊነቴ እንድኮራ ያደርገኛል፡፡የድሉ ባለታሪክ ባልሆንም ይነሽጠኛል፡፡ጀግኖች አባቶች ጠላታቸው ምን መሣሪያ ታጥቆ እንደመጣ እና ምን ያህል ኃይል እንዳለው እንኳን ሳያውቁ ሀገራችንን አናስደፍርም ብለው ከ1ሺ ኪሎሜትር በላይ በዱር በገደሉ በእግራቸው ተጉዘው ሀገራችንን አናስደፍርም ብለው መስዋዕትነት የከፈሉ መሆናቸውን ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡በድላቸውም እኮራለሁ»ሲሉ ታሪኩን ያወሳሉ፡፡የዓድዋው ጦርነትና ድል ኢትዮጵያ የሰውን የማትፈልግ፣ሀገር ሊወር የመጣን ጠላት ለማሳፈር በአንድነት ሆ! ብሎ የሚነሳ ጀግና እንዳላት ተምሳሌት እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡
በዓድዋው ጦርነት ላይ የነበሩት ጠላትን ድል ለማድረግ በመካከላቸው የነበረው የቋንቋና የኃይማኖት ልዩነት ያላለያያቸው ጀግኖች እንደነበሩ የገለፁት ልጅ ዳንኤል ጀግኖች አባቶች ለመሾም፣ወይም የተለየ ጥቅም ለማግኘት እንዳልነበረና የሀገር ፍቅር አንድ እንዳደረጋቸው ያስረዳሉ፡፡በጠላት ተመትቶ የወደቀው እንኳን ከራሱ ይልቅ ሀገሩን በማስቀደም ከወደቀበት ሊያነሳው የሚሞክውን ወገኑን ግዳጁን እንዲወጣ ይገፋፋው እንደነበርም ከታሪክ የሰሙትን ነግረውናል፡፡የዓድዋው ድል ዓለምን ያስደመመ ለመላው አፍረካ ኩራት የሆነ ገድል የተገኘበት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ከዓድዋ ድል ጀግንነት ብቻ ሳይሆን ትብብርና አንድነት የታየበት፣ እንዲሁም ትልቅ ትምህርት የተገኘበት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች ዓርበኞች ማህበር የሥራ አመራርና አስተዳደር ምክር ቤት አባል አባት ዓርበኛ ዳኛቸው ተመስገን አንድ መቶ ዓመት ዕድሜ ያስቆጠሩ እናታቸው ታሪክ እንዳወረሷቸውና እርሳቸውም በንባብና በተለያየ አጋጣሚ ስለዓድዋ ታሪክ ለማወቅ ዕድሉን አግኝተዋል፡፡
ስለዓድዋ ድል ታሪክም እንደገለጹልን «ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ መገኘቷ፣መልክዓ ምድሯም ሆነ የአየር ጠባዩዋ ተስማሚ በመሆኑ ሁሉም ዓይኑን ያሳርፍባታል፡፡በመሆኑም ጣሊያን ይህን ሀብቷን ቋምጦ ዘመናዊ ጦር መሣሪያ ታጥቆ በአየር ጭምር በመታገዝ ነበር በኃይል ሊወርር የመጣው ግን አልሆነለትም፡፡ ጀግኖች አባቶች ግዙፉን የፋሽስት ጣሊያን ጦር ባልተደራጀ መሣሪያ ነው አሳፍረው ከሀገራቸው ያስወጡት»
በአጠቃላይ ስለጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች ዓርበኞች ማህበር አደረጃጀትም እንዳስረዱት የዓርበኝነት ታሪክ በሦስት ይከፈላል፡፡ዓርበኛ፣የውስጥ ዓርበኛና ስደተኛ በሚል ይከፈላሉ፡፡ዓርበኝነት ከኢትዮጵያ ሳይወጣ በሀገር ውስጥ በግንባር የተዋጋ ሲሆን፣የውስጥ ዓርበኛ ማለት ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ የገባን ጠላት እራስን እየቀያየሩ ለጠላት የተሳሳተ የመረጃ አቅጣጫ በመስጠት፣ለዓርበኞች ደግሞ ጠላት የሚመጣበትን አቅጣጫ በመጠቆም ጠላት እንዲደመሰስ በማድረግ በጦርነቱ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ናቸው፡፡ስደተኛ ማለት ደግሞ በጠላት አልገዛም ብሎ በጎረቤት ሀገሮች ሸሽቶ ግን ባለበት ሆኖ ለጦሩ አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ ነው፡፡
ከታሪክ ድርሳናት ያገኘነው መረጃ እንደሚ ያመለክተው የዛሬ 122ዓመት ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በግፍ ሊወርር በመጣበት ጊዜ አፄ ሚኒልክ በአራቱም ማዕዘን የሚገኘው ህዝብ ያለውን የጦር መሣሪያ ይዞ በጠላት ላይ እንዲዘምት የክተት አዋጅ ሲያወጁ«...ወስልተህ የቀረህ ሁሉ አልምርህም...» ያሉት አይረሳም፡፡የውጫሌው የአንቀፅ 17 የውል ስምምነት የአማርኛውና የጣሊያንኛው ፍች አንድ አለመሆን ለጦርነቱ ምክንያት እንደሆነም ይታወሳል፡፡ የዓድዋው ጦርነት ከአንድ ቀን በላይ የፈጀ አለመሆኑም በታሪክ ተዘክሯል፡፡

ለምለም መንግሥቱ 

 

 

 

 

ወቅታዊው የፖለቲካዊ ችግር እና መፍትሄዎቹ

ይህን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ምክንያት የሆነኝ ሠሞኑን የአሜሪካን ኤምባሲ ያወጣቸው ሁለት እርስ በእርሳቸው የሚቃረኑ መግለጫዎችን በ VOA ማዳመጤ ነው። በእርግጥ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ እንደማናቸውም ኢትዮጵያዊ የሚያስጨንቀኝ ጉዳይ ቢሆንም ከሚመስሉኝ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ከመወያየት ባለፈ በጋዜጣ ላይ ይህን መጣጥፍ ለማዘጋጀት የመንፈስ ዝግጅት አልነበረኝም። የኤምባሲው መግለጫዎች በዚሁ ወቅታዊው የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረም ነበር።
የአሜሪካ ኤምባሲ መግለጫ


የመጀመሪያው እና ቀድሞ የተገለጸው በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ወቅታዊ የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት የአሜሪካ ዜጐች በአገሪቱ ውስጥ የሚያደርጉት እንቅስቃሴን በመደበኛ ወቅቶች ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ በተለየ መልኩ ጥንቃቄ በማድረግ እንዲንቀሳቀሱ፣ ግጭቶች ከሚታዩበት አካባቢ እራሳቸውን እንዲያርቁ፣ መንግሥት የሚያወጣቸውን መግለጫዎች በመከታተል ይህንንም እንዲያከብሩ በሚል የዜጐቹን ደህንነት ለመጠበቅ እንዲረዳ ያደረገው መንግሥታዊ ኃላፊነት ተገቢም ትክክለኛም በመሆኑ የምቀበለው ነው። በተለያዩ ጊዜያት ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ችግር አለ ብሎ በሚያምንበት ወቅት ሁሉ ዜጐቹ ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉዞ እንዲያቅቡም ሲገልጽ መቆየቱ የሚታወስ ነው። የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቢሆን በአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ ተመሳሳይ ችግር አለ ብሎ በሚያምንበት ወቅት ሁሉ በአሜሪካ ለሚኖር ዜጐቹ ተመሳሳይ መግለጫ በማውጣት ዜጐቹን ጥበቃ ሊያደረግላቸው የሚጠበቅበት ኃላፊነቱ ነው።


ሁለተኛው እና የዚህ ፀሐፊን ትኩረት የሳበው የሚኒስትሮች ም/ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማውጣት ያሳለፈውን ውሳኔ አስመልክቶ ኤምባሲው ያወጣው መግለጫ ነው። ኤምባሲው ከአገሪቱ ሕገ-መንግሥት እና ሕግ ወጣ ባለ መልኩ በአንድ ሉአላዊ አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት መግለጫ ማውጣቱ አንድም ከዲፕሎማሲ አኳያ በሌላ በኩልም ኢትዮጵያ እራሷን የቻለች ሉአላዊ አገር ከመሆኗ ጋር በተያያዘ በውስጥ ጉዳይዋ ገብቶ ይህን አድርጉ ይህን አታድርጉ የሚል የቀድሞ ቀኝ ገዢዎች በአፍሪካ ያደረጉትን እንደነበረው አይነት ተግባር ውስጥ መታየቱ በእጅጉ የሚያሳዝን ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተቃውሞ ድምፁን ማሰማት አሊያም አምባሳደሩን አስጠርቶ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ መጠየቅ ሲፈጽም ባለማየቴ እንደ አንድ ዜጋ አርፋችሁ አፋችሁን ዘግታችሁ ተቀመጡ። ይህ የኛ የኩሩ ኢትዮጵያውያን ብቸኛ መብት እና መብት ነው። የራሳችን ጉዳይ በራሳችን ላለፉት ሦስት ሺህ ዘመናት እየወሰንን የመጣን ትልቅ ታሪክ ያለን ሕዝቦች ነን በመሆኑም በውስጥ ጉዳያችን ገብታችሁ ልትፈተፍቱ አይገባችሁም ማለት እወዳለሁ።
እናንተ የዜጐቻችሁ ደህንነት እንዲጠበቅ እዚህ አትሂዱ ይህን አታድርጉ እያላችሁ ባላችሁበት ሁኔታ የአገሪቱ ሠላምን በመደበኛ ሁኔታ ማስጠበቅ አልተቻለም በሚል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣታችን ችግሩ ምንድን ነው? ጉድለት ቢኖረው እና አግባብ ባለመሆኑ መስተካከል ይገባዋል ብለን ድምፃችንን ማሰማት የኛ ብቸኛ ሥልጣንና ኃላፊነት አይደለምን? በዋሽንግተን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በጥቁር አፍሪካን አሜሪካኖች ላይ የሚካሄደውን ዘረኝነት እና በፕሬዚዳንት ትራምፕ መንግሥት ስደተኞች (ኢሚግራንት) አፍሪካውያንን አስመልክቶ የሚያወጣው መግለጫ ላይ የተቃውሞ ምላሽ ቢያወጣና በእናንተ የውስጥ ጉዳይ ገብቶ ቢፈተፍት ተገቢ ተግባር አድርጋችሁ ታዩታላችሁን?


በእውነት የአሜሪካን ኤምባሲ በኢትዮጵያ ስለሚካሄደው ዴሞክራሲያዊ ሂደት ያን ያህል የሚጨነቅ ከሆነና በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ለመግባት የሚያስችለው ሁኔታ ካለ በቅርቡ የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ባልተለመደ ሁኔታ ከማናቸውም ተቃዋሚ ኃይሎች ጋር በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ከሚገኙት ጋር ለመነጋገር ዝግጁ ነኝ በሚል የሰጠው መግለጫን በመደገፍ ጉዳይ ፍሬያማ ሆኖ እንዲወጣ እገዛ ለማድረግ ተነሳሽነቱን ለማሳየት እንደምን ተሣነው? ወይም አሜሪካ በቅርብ እየተቆጣጠረ የሚመራው የዴሞክራሲያዊ ሂደት በኢትዮጵያ ካልተካሄደ ቢቀር ድምፁን አያሰማም ማለት ነው። በዚህ ረገድ እኔ የሰማሁት ነገር የለም፣ እናም ምላሹን ለእናንተ ትቼዋለሁ። ለነገሩ የአሜሪካ የራሱ ዴሞክራሲ ምን ያህል አደጋ ላይ እንዳለና የቁልቁል ጉዞ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ የሚፈልግ JANE MAYER በ2016 የፃፈችው DARK MONEY የሚለውን መጽሐፍ የሚያነብ ሁሉ ያለበትን ሁኔታ በቀላሉ ሊረዳው ይችላል የሚል እምነት አለኝ።


እንዲህ የአገራችን ፖለቲካ ከዓለም በተለይም ከአሜሪካን ተጽዕኖ ነፃ እንዳልሆነ ባለፉት ዓመታት ያየነው ጉዳይ ነው። በመሆኑም ከዚህ መሠሉ ውጥንቅጥ ወጥተን ሉዓላዊነታችንን ሣናስደፍር በምን መልኩ ስኬታማ የፖለቲካ ሥርዓት በመዘርጋት ሰላማዊ ሽግግር ላይ መድረስ እንችላለን የሚል ጉዳይ ዋነኛው የትኩረት አቅጣጫ ስለሆነ በግርድፉ ያለፈ የፖለቲካ ታሪካችንን በመቃኘት በአሁኑ ወቅት አገሪቱን ቀስፎ የያዛትን ወቅታዊ ፖለቲካዊ ችግር እና መፍትሄዎቹ ላይ ያለኝን የግል አስተያየት በዚህ ጽሁፍ ማጠቃለያ ላይ አስቀምጣለሁ።


የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና እንደምታው


በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ሠላም የማስከበር ጉዳይ በመደበኛው ሁኔታ መፈጸም እንዳልተቻለ መንግሥት ካወጣው መግለጫ መረዳት ችለናል። ጉዳዩ እውነት ያለው መሆኑን በግላጭ እያየነው ያለ ሃቅ በመሆኑ የአዋጁ መውጣት የሚያጠያይቅ አይመስለኝም፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ በመደበኛነት መፈፀም ያልቻለው የአገሪቱ ሠላም ብቻ ሣይሆን የዴሞክራሲያዊ መብቶችን አጠቃቀምም ከ1997ዓ.ም ምርጫ በኋላ በመደበኛ መልኩ እየተፈፀመ ሣይሆን በርካታ ችግሮች ውስጥ ገብቶ የቆየ በመሆኑ ይህም ጉዳይ ትኩረት የሚሻ ነው የሚል ሃሣብ በፀሃፊው ዘንድ አለ።
የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አገራችን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ በገመገመበት ወቅት በግልጽ እንዳስቀመጠው የህዝባችን ዴሞክራሲያዊ መብት አያይዘን በጥልቅ በመመርመር ያሉበትን ችግር ማረም እንደሚገባ እንደዚሁም በወጣቶች እየተነሱ ላሉ ተገቢ ጥያቄዎች በአግባቡ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ የተገለፀ ሲሆን የተደረሰበት ድምዳሜና ያሣለፋቸው ውሣኔዎችም ዴሞክራሲ የህልውናችን መሠረት ነው የሚለው መርህ ላይ ያለው አቋምን በግልፅ ያመላከተበት ነበር።


በመሆኑም ፓርላማው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአቀረበውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲመረምር ሠላም ማስከበር እጅግ ወሣኝ የመሆኑን ያህል የፖለቲካ ምህዳሩ የሚጠብበት ሁኔታ እንዳይፈጠር እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚያረጋግጡ ህገ-መንግሥታዊ መብቶች ላይ የሚጣል ገደብን ለመከላከል አፅንኦት ሠጥቶ ሊመለከት ይገባል።
የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ በመገደብ የአገሪቱን ፀጥታ እና ሠላም ለማስፈን ጥረት ከማድረግ ይልቅ በአሁኑ ወቅት የምናየው መሪ ድርጅት የሌለው የተበታተነ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በስርዓት እንዲመራ ፍላጐቱና ፈቃደኛነቱ ያላቸው ሃይሎች ከፈለጉ በተቃዋሚ ድርጅቶች ሥር ተሠልፈው የህጋዊና ሠላማዊ ትግሉ አካል እንዲሆኑ ማበረታታት አንዱ ሲሆን ተቃዋሚ ድርጅቶችም እንደማናቸውም ህጋዊ አካል በየአካባቢያቸው የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎችን ህጋዊና ሠላማዊ እንዲሆኑ ኃላፊነት በመውሰድ የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ሠላም የማስፈኑ አንዱ አካል ማድረግ ይቻላል። በመሆኑም የተወካዮች ምክር ቤት ይህን እና መሠል አማራጮችን ሁሉ በማገናዘብ ሠላማችንን ለማምጣት የሚያስችል አዋጅ ማውጣት ይገባዋል የሚል አስተያየት መስጠት እወዳለሁ፡፡


የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን መልቀቅ


ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ የደረሰው የፖለቲካዊ ቀውስ ደረጃው ከፍ ያለ የብዙ ዜጐችን ህይወት የቀጠፈና ከግማሽ ሚሊዬን በላይ ህዝብ የተፈናቀለበት ክስተት መሆኑ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ሣይሆን እንዳለ መንግሥታቸው ከሃላፊነት እራሱን በማግለል የሥልጣን መልቀቂያ የማቅረብ እርምጃ ሊወስድ ይገባ ነበር። ይህም ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻቸውን ለችግሩ ኃላፊነት በመውሰድ እራሳቸውን ከሥልጣን ለማውረድ ጥያቄ ማቅረባቸው ሊያስመሰግናቸው እና ክብርም እንድንሠጣቸው የሚያደርገን ይሆናል።


ይህ እንዳለ ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አድርሰውታል ለተባለው ድክመት ምክንያት በሆነው ጉዳይ ላይ የተለየ ሃሣብ እና አቋም አለኝ፡፡ ኢህአዴግ ከትጥቅ ትግል ዘመኑ ጀምሮ እየተከተለ የመጣው የአመራር ሥርዓት በግለሠብ ላይ የተማከለ ሳይሆን የቡድን ወይም የኮሚቴ አሠራርን የሚከተል ሆኖ እናገኘዋለን። ይህ ዓይነቱ አሠራር የግለሠብ ሚናን ዝቅ የሚያደርግ ተጠያቂነትም ላይ በውል ኃላፊነትን የሚወስድ ግለሠብ እንዳይኖር የሚያደርግ በመሆኑ ግልፅነት የጐደለው አሠራር ሆኖ እናገኘዋለን። የፖለቲካ ፓርቲን ለመምራት ወይም የትጥቅ ትግልን ለማካሄድ እንዲህ አይነት አሠራር ተገቢም ውጤታማም ሊሆን ይችላል። በመንግሥት መዋቅር አሠራርና በአገር አስተዳደር ደረጃ እንዲሁም በዘመናዊ የማኔጅመንት ትምህርት እንዲህ መሠሉ የአስተዳደር ዘይቤ በመርህ ደረጃ ተቀባይነት የሌለው ሆኖ እናገኘዋለን።


ኢህአዴግ የመንግሥት ሥልጣን ይዞ ባለበት ሁኔታም አገር እያስተዳደረም የሚከተለው የአስተዳደር ሥርዓቱ በትጥቅ ትግሉ ወቅት በነበረበት ሁኔታ እንዲቀጥል በማድረጉ የችግሮቹ ሁሉ ምንጭ ሊሆን ችሏል የሚል አመለካከት አለኝ ፡፡የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስተዳደር እስከ 1993 የህወሓት ክፍፍል ድረስ ይህን መሠል አሠራር በመከተሉ ውጤታማ የመንግሥት አስተዳደር የጠራ ፖሊሲ እና እስትራቴጂ ሊኖረው አልቻለም ነበር ፡፡ መንግሥታቸው በውጤታማነትም ሆነ የኢኮኖሚ ዕድገትን በግልፅ ማስመዝገብ የቻለው በድህረ-ህወሓት ክፍፍል ነበር ቢባልም ማጋነን ተደርጐ የሚወሰድ አይደለም ፡፡


ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሣለኝም የዚህ አሠራር ሠለባ በመሆናቸው የሥራ ትጋትና ውጤታማነታቸውን እንዳናይ በቡድን አመራር እንዲሸፈኑ ምክንያት ሣይሆን አልቀረም። እዚህ ላይ ልብ ማድረግ ያለብን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ማነፃፀሪያ አድርጐ መውሰድ እጅግ እጅግ የተሣሣተ ድምዳሜ ላይ ይጥላል። የእርሣቸው ችሎታ በልዩ ሁኔታ የሚታይ ጉዳይ በመሆኑ አቶ ሃይለማሪያምን ለመመዘኛነት መጠቀም አንችልም። አቶ ሃይለማሪያም ደሣለኝ በጐ ጐኖችን ለማንሣት ያህል በሙስና ሥማቸው የማይጠራ መሆናቸው አንዱ ሲሆን በተመሣሣይ የአዲሱ ወጣት ትውልድ አካል በመሆናቸው በዙሪያቸው ከምናያቸው ሁሉ የተሻሉ እንደሆኑ በትምህርት ዝግጅታቸውም ሆነ የሥራ ልምዳቸው በቂ ምስክር ነው ማለት እንችላለን።


ሌላው የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሣለኝ ጥንካሬ በተለይ በቅርቡ ያዋቀሩት ካቢኔአቸው ጥንቅርን ስናይ ከሞላ ጐደል የተዋጣለት ሥብሥብ እንዳለው መናገር ይቻላል። የመንግሥት ቃል አቀባዩ ከማናቸውም ከሣቸው በፊት ከነበሩት እጅግ ጐልተው የወጡ ችሎታቸውንም በመድረክ በግልጽ ያሣዩ ሃላፊ አስቀምጠውልናል፡፡ የውሃ፣መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩም ቢሆኑ ባለፉት ሃያ ዓመታት ከነበሩት እጅግ ብቃት ያላቸው ሠው ናቸው። የግብርና ሚኒስትሩም እንዲሁም የሣይንስ እና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ሌሎቹም ያላነሣኋቸው በጥንካሬ የሚገለፁ ናቸው። እንግዲህ ይነስም ይብዛም ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም በ1983 ዓ.ም የሽግግሩ መንግሥት ጊዜ ከነበረው ካቢኔ ቀጥሎ የተሻለ ካቢኔ አቋቁመው ሥራቸውን ለማሣካት ጥረት እያደረጉ ባለበት ሁኔታ አገሪቷ የገጠማት ቀውስ ለዚህ ችግር አብቅቷቸዋል፡፡በእርግጥ ቀውሱን ለመምራት እና በቁጥጥር ሥር ለማዋል ዋናው ተግዳሮት የሆነባቸው የሚመስለኝ የእርሳቸው የአመራር ብቃት ማነስ ሣይሆን የቡድን አመራሩ የፈጠረው ክፍተት ያመጣው ጣጣ ይመስለኛል።


ለቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር አሁን ያለውን የቡድን አመራር ሥርዓት በማስቀረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኃላፊነት የሚጠየቁበት ሙሉ ሥልጣን እንዲኖራቸው እና የሥራቸውን እንቅስቃሴ ደግሞ የተወካዮች ምክር ቤት አሁን ካለው ሥልጣን ከፍ ባለ ሁኔታ እየተከታተለ እንዲቆጣጠራቸው በማድረግ ሙሉ ሃላፊነት እና የተጠያቂነትን አሠራር በማለፈና በዚህ ሁለት ዓመት የሚገኝ ተሞክሮን በመቀመር በቀጣይ የአመራር ሥርዓቱን ለማዘመን እንደ ትምህርት የሚቀስምበት መድረክ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል ማለት ነው።


ወቅታዊ የፖለቲካዊ ችግር እና መፍትሄዎቹ


በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ የመንግሥት ሥልጣን የመጋራት ጉዳይ ዋነኛው ችግር ሆኖ ኖሯል ፡፡ በመካከለኛው ዘመን የነበሩ መንግሥታት ስልጣን ላለማካፈል ልጆቻቸውን በባላንጣነት ያዩ ስለነበር በገዳማት አካባቢ ተገልለው በቁም እስረኝነት ጊዜያቸውን እንዲጠብቁ ይደረግ ነበር። በቅርቡም ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በእድሜ ጃጅተው አገር መምራት ባቃተቻቸው ወቅት እንኳ ሥልጣናቸውን ለልጃቸው የማጋራት ፈቃደኛነት እንደጐደላቸው ያየነው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። በተመሳሳይ የደርግ መንግሥት ጠመንጃ በታጠቁ አማጽያን ተወጥሮ በተያዘበት በ1982 እንኳን ለቀረበለት የድርድር ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ተስኖት ሲያላግጥ እጣ ፈንታው ምን እንደሆነ የምናውቀው ሃቅ ነው። በመሆኑም ፖለቲካዊ ችግሮችን በውይይት እና በድርድር ተቀራርቦ በመነጋገር የመፍታት አንዳችም ልምድ እንዳልነበረን መገንዘብ ይቻላል።


የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባለፉት 27 ዓመታት ያሳለፈውን ሂደት ስንገመግም ደግሞ የችግሮቻችን ምንጭ ሆኖ የምናገኘው ያው የፖለቲካ ባህል ችግር ሆኖ እናገኘዋለን። ኋላ ቀር በሆነው የፊውዳል ሥርዓት ውስጥ ተወልደን ያደግን በዚህም ባህል ተኮትኩተን ያደግን መሆናችን በትምህርት እንኳን መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት ሣንችል እንድንቀር አድርጐናል። በዚሁ ሁኔታ ወደ ሥልጣን የመጣው የኢህአዴግ መንግሥት በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመዘርጋት የሞከረበትን ሁኔታ ካለን የፖለቲካ ባህል ደካማነት አንፃር ፍሬ ማምጣት እንዳልቻለ ምርጫ 97 ጥሩ ማሣያ ተደርጐ ሊወሰድ የሚችል ይመስለኛል።


ምርጫ 97 ውጤቱ ምንም ይሁን ምን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተፈፀመ እንደነበር ይታመናል። የተቃዋሚውም ኃይል ሆነ ገዢው ፓርቲ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እናደርጋለን የሚል እንጂ የሚመጣውን ውጤት ለመቀበል ዝግጁነቱ የነበራቸው አይመስልም ነበር። በመሆኑም ያን መልካም አጋጣሚ ባዶ ሜዳ ላይ ባክኖ እንይቀር ሁሉም የድርሻውን ተወጥተዋል ማለት ይቻላል። ይህን በመሠለ ዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመተዳደር ኢትዮጵያውያን ዝግጁነቱ ይጐድላቸዋል ስለሆነም ጠንከር ያለ አውራ ፓርቲ በመፍጠር ልማትን ማስፋፋት የተሻለው አማራጭ ነው የሚል አስተሳሰብ የሚያቀነቅኑ በዋነኛነት ከዲያስፖራው የመጡ ጽንፈኞች በኢህአዴግ ዘንድ ተሰሚነት ማግኘታቸው ደግሞ ባለፉት አሥራ ሦስት ዓመታት የአውራ ፓርቲ ትኩረት እንዲያገኝ ሲያደርግ የፖለቲካ ምህዳሩን ጨምድዶ በመያዝ ፓርላማውን በሙሉ እስከ መቆጣጠር የደረሰ ሁኔታ ውስጥ ለመግባት በቃን።


ይህ ሁኔታ የፈጠረው ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት እና መሠረተ ሠፊ የሆነ የሙስና መረብ ተዘርግቶ ኢኮኖሚውን ውል ሲያሳጣው መንግሥት በጥቂት ኃይሎች እጅ ሥር እንዲወድቅ ምክንያት ሆነ ፡፡ በሁኔታው ግራ የተጋቡት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በፓርላማ ቀርበው በአንድ ወገን በመንግሥት ውስጥ ባሉና በሌላ በኩል ከመንግሥት ውጪ ያሉ ኃይሎች ተቀናጅተው መንግሥትን እጅና እግር ጠፍረው በመያዝ መንቀሳቀስ እንዳቃታቸው እስከ መግለጽ የደረሱበት ሁኔታ ተፈጥሮም ነበር። ሁኔታው ከጠቅላይ ሚኒስትሩም ሞት በኋላ እጅግ ተጠናክሮ በመቀጠሉ ሕዝቡ ሁኔታውን መሸከም የማይችልበት ደረጃ ላይ ደረሰ። ይህም ከ2008 መጀመሪያ ጀምሮ ባልተደራጀ መልኩ በተለይ በሁለት ክልሎች አመጽ በየአቅጣጫው ተቀጣጥሎ አገሪቱን ቀውስ ውስጥ ሲከትታት ኢኮኖሚዋንም ወደ ከፋ ጐዳና እንዲገባ እያደረገው ይገኛል።


በመሆኑም አገሪቱ ከዚህ አጣብቂኝ እንድትወጣ ያለው ብቸኛ አማራጭ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ ፖለቲካዊ ምህዳሩ ቅድመ ምርጫ 97 የነበረበት ሁኔታ ላይ እንዲመለስ ማድረግ እንደሚገባ ፀሐፊው ያምናል። በዚህም ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አሣታፊ የሆነ የፖለቲካ ሥርዓት መዘርጋት የሚቻል ሲሆን ይህን መደላድል ለመፍጠር የፓርቲዎች የድርድር መድረክ መፍጠር የሚገባ ይሆናል፤ ባዕዳንን ለታዛቢነት እንኳን ሣንጋብዝ ፍፁም ኢትዮጵያውያን ብቻ የሚሳተፉበት ሂደቱንም ለመከታተል እንዲቻል የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችን እና ያገባናል የሚሉ ዜጎች በሙሉ የሚሳተፉት ሁኔታን በማመቻቸት መጪው 2012 ምርጫ ድረስ የፖለቲካ ምህዳሩን የምርጫ ሕጉን እና ሥርዓቱን እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ በአሸናፊ ተሸናፊ መንፈስ ሣይሆን ሁሉም የሚያሸንፉበት ሠጥቶ የመቀበል መርህን የሚከተል አቅጣጫን በማስያዝ ይህን ሁኔታ ወደ መልካም አጋጣሚ መለወጥ መቻል ይገባል።


ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ዛሬ የሚያስፈልጋት ጥገናዊ ለውጦች (Reform) እንጂ አብዮት(Revolution) መሆን አይገባም የሚል አስተሣሠብ በዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ዘንድ አለ። አገሪቱ ባለፉት አርባ አምስት ዓመታትን ሁለት Revolution (አብዮቶች) አካሂዳለች። በዚህም ቀላል የማይባል ዋጋን አስከፍለውን ያለፉ ጉዳዮች መኖራቸው እሙን ነው። በእርግጥ አብዮቶቹ እጅግ መሠረታዊ የሆኑ ለውጦችን ያስገኙ ቢሆንም የተረጋጋ እና ቋሚ የሆነ መንግሥት በመመስረት ረገድ አላስፈላጊ ደም መፋሠሶች እና ሌሎች ችግሮች ሣይገጥሙን ተከታታይ የሆኑ ጥገናዊ ለውጦች (Reform) በማካሄድ በተሻለ ሁኔታ የምንፈልጋቸው ለውጦችን እና የማሻሻያ እርምጃዎችን ማድረግ እንችል ነበር።


መንግሥት አገሪቱ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ እንደምትገኝ ከመግለፁም በተጨማሪ ለቀውሱ መፍትሄ ይሆናሉ በሚል በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞችን በይቅርታ እና በምህረት በመፍታት ረገድ የወሰዳቸው እርምጃዎች በእጅጉ አድናቆትን ሊያስቸረው የሚገባ ጉዳይ ነው። ይህን መሠሉ ጉዳይ ለሠላም የሚከፈል ዋጋ በመሆኑ ሁሉም ወገኖች ድጋፋቸውን ሊቸሩት ይገባል። በተመሣሣይ ሁኔታ ከእስር የተለቀቁት ሁሉም ታራሚዎች እጅግ ባልተለመደና አርቆ አሣቢነትን በሚያሣይ መንገድ ከእስር በወጡበት ወቅት በሠጧቸው መግለጫዎች ያለፈ ቁስል የማንሳት ጉዳይ ላይ ሣይሆን ስለቀጣይ የአገሪቱ ሠላማዊ የፖለቲካ ትግል አስፈላጊነት እና በማናቸውም የተቃውሞ ወቅት ንብረት ማውደም እና የሠው ህይወት በሚቀጥፍ መልኩ የሚፈፀም ተግባር መኖር እንደሌለበት በመግለፅ መብሰልና መረጋጋትን ማሣየታቸው ታላቅ አክብሮትና አድናቆት ልንቸራቸው ይገባል። ይህን ሁኔታ ከቅዳሜው የኢቲቪ የሚዲያ ዳሰሳ ፕሮግራም ውጪ ሌሎች የመንግሥት ሚዲያዎች አጉልተው በማውጣት የመቻቻል ፖለቲካ በአገራችን እንዲዳብር ሊጠቀሙበት ሲገባ ያመለጠ አጋጣሚ ሆኖ አልቋል።


እነዚህ ከላይ ያነሣናቸው ሁለት አብነቶች የአገራችን ፖለቲካ ከጥላቻ ወደ መቻቻል መሸጋገር እንደሚችል ፍንጭ ሠጪ ሆነው በማግኘቴ ያቀረብኩት ሲሆን ይህም እየዳበረ ሲሄድ ከገባንበት አጣብቂኝ እየወጣን በሠለጠነ ፖለቲካ የመንግሥት ሥልጣን የመጋራት እንዲሁም በምርጫ የሠላማዊ ትግል የፖለቲካ ሥልጣን ሽግግር በአገራችን ማድረግ እንደምንችል ለዓለምም ለአፍሪካም ማሣየት የምንችልበት መሆናችንን ለማሣየት ነው። ከዚህ በተጨማሪ ወጣቱ ትውልድ ይህን አዲስ የፖለቲካ ባህል ውርስ የወደፊት ኢትዮጵያን የፖለቲካ ሥልጣን በሠላማዊና በሕዝብ ፈቃድ ተመስርቶ የሚገኝ መሆኑን የልምድ ልውውጥ የምናረጋግጥበት ይሆናል በሚል ተስፋ የቀረበ ጽሁፍ ነው።

ሮባ ቶክቻው

Published in ፖለቲካ

ዘንድሮ የአድዋ ድል 122ኛ ዓመት ነገ በታላቅ ድምቀት በብሔራዊ ደረጃ ይከበራል፡፡ ወራሪውን የኢጣሊያን ፋሽስት ሠራዊት በአጼ ምኒልክና በእቴጌ ጣይቱ የሚመራው ከመላው ኢትዮጵያ ተውጣጥቶ ክተት አዋጆ ነጋሪት ጎስሞ የዘመተው የኢትዮጵያ ሠራዊት ረዥምና አድካሚ መንገድ በእግር ተጉዞ ወንዙን ተራራውን ሸለቆውን አቋርጦ በአብዛኛው ቤት ያፈራውን ስንቅ ዳቦ ቆሎውን ይዞ በየጦር መሪና አዝማቹ በመመራት በተሰጠው ግዳጅ ጉዞውን ወደአድዋ አደረገ፡፡
በአድዋ ቁልፍ ወታደራዊ መሬቶች መሽጎ በዛን ዘመን ምርጥ የተባለ ሠራዊቱንና የጦር መሳሪያውን የተማመነው የጥቁር ሀገር ሠራዊት እኔን ሊመክተኝ አይችልም በሚል እብሪት የተወጠረው በምርጥ የኢጣሊያን ወታደራዊ ጄነራሎች የሚመራው የዘመኑን ታንክና መድፍ የጦር አውሮፕላን የታጠቀው የፋሽስት ኢጣሊያ ሠራዊት ከበቂ በላይ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡
በአድዋ በመረጠው ወታደራዊ መሬት ላይ በጥልቀት የተቆፈረ ምሽግና በየአቅጣጫው ሊመጣ የሚችለውን አጥቂ ኃይል መምታት የሚችል የተጠመደ መሣሪያ፤ በቂ ስንቅና ትጥቅ፤ ቁልፍ ወታደራዊ መሬት፤ ተጠባባቂና ተደራቢ የተለያዩ ክፍለጦሮችን አስቀድሞ ቦታ በማስያዝ ባዘጋጀው ወታደራዊ የዘመቻ እቅድ ሙሉ በሙሉ በንጉሠ ነገሥቱ የሚመራውን የኢትዮጵያ ሠራዊት በየቦታው ከፋፍዬ ቆራርጬ እደመስሰዋለሁ ብሎ ተኩራርቶ ነበር፡፡ ኢጣሊያኖች እጅግ እንደ ነበልባል የሚንተገተገውን ለሀገራቸው ክብር ለመሞት ቁርጠኛ ውሳኔ ያላቸውን የአበሾች ወኔ አላወቁትም፡፡ አይቶ ነው ገምቶ ነው መውረድ ኋላ ከመዋረድ የሚለውን የአበሾች አባባልም አላወቁትም፡፡
በኢትዮጵያ ወገን በአብዛኛው ባሕላዊ ጦር መሳሪያ ጋሻና ጦር የያዘ በተረፈ ብዙም ዘመናዊ ያልሆኑ የጦር መሳሪያዎች መድፎችና መትረየሶች አጤ ምኒልክ ከውጭ ሀገር በግዥ ያስመጡዋቸውን የታጠቀ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ለተዋጊው ሠራዊት በምግብ ማብሰል በውጊያው ሲቆስል ለማከምና ለመንከባከብ እንዲሁም በተዋጊነት አብረው ተሰልፈዋል፡፡ የቤተክህነት ቀሳውስት ጭምር አብረው ዘምተዋል፡፡
ውጊያው ተጀምሮ ከተካሄደ በኋላ የኢትዮጵያውያን ፍጹም ጀግንነትና ሞት አይፈሬነት የዛ ሁሉ ቀላልና ከባድ መሳሪያ ጥይት እየዘነበ ሞትን ተጋፍጠው የወደቀውን እየተረማመዱ የኢጣሊያንን አንገት በጎራዴ እየቀሉ በደረቱም ላይ ጦር እየሰኩ በደም እየዋኙ ገላቸው በደም ረስርሶም እየፎከሩና እያቅራሩ በፍጹም የሞራል የበላይነት የፋሽስቱን ሠራዊት ምሽግ እየደረመሱት ገቡ፡፡ የሚመክታቸውም ሆነ የሚገታቸው ኃይል ከቶውንም አልተገኘም፡፡ ቀረርቶው ሽለላው ወኔ የሚቀሰቅስ እምቢ ለሀገሬ እምቢ ለእናቴ የሚል ነበር፡፡
እናት አባት ቢሞት--- በሀገር ይለቀሳል፤
ሀገር የሞተ እንደሁ-- ወዴት ይደረሳል፤
ባንዳ ገዳይ----- ሰላቶ ገዳይ፤
በደም አባላ--- ከአውድማው ላይ፤
አነባባሪ መቱን---- በተርታ፤
ጥቁር ግስላ---- ጥቁር አንበሣ፣የጦሩ ጌታ፤
እናቱ ትኩራ--- የወለደችው፤
አማቹም ትኩራ----- የተጋባችው፤
ሀሞተ ኩሩ--- ልበ ኮስታራ፤
ለፋሽስት ጦር ---ልቡ እማይራራ፤
በለው ሲል ገዳይ---እርሳስ ሲዘራ፤
አነባባሪ ----ተራ በተራ፤
የጦር አጎዳ -- የአውድማው አውራ !
እያሉ በየቋንቋቸው እየፎከሩ የሞራል ጥጋቸው በአድማሱ ላይ ናኝቶ በጠላት አንገት ላይ ጎራዴያቸውን እያሳረፉ ጥለውታል፡፡ያን እለት ምድር አርግዛ ምጥ የያዛት እለት ቀውጢ ስትሆን እሳት ሲበላት---ሰላቶ መውጪያ ሲታጠርበት እያለ በዚህ የላቀ ሞራል ሙሌት እየተንቆራጠጡ የወደቀው ወድቆ ጠላት ምሽግ ላይ የደረሱት ኢትዮጵያውያን ጀግኖች የፋሽስቱን ሠራዊት ባለበት ምሽግ ገብተው ፈጅተውታል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ታላቅ የማይበገር ሞራልና መንፈሳዊ ልእልና ባለቤትነትም ነው፡፡ የአይበገሬዎቹ ሀገር ኢትዮጵያ እንዲህ ናት፡፡ሞትን ንቀው ለክብራቸውና ለነጻነታቸው ደረታቸውንና ግንባራቸውን አሳልፈው የሰጡ የእልፍ አእላፍ ጀግኖች ምድር ኢትዮጵያ፡፡የዛ ሁሉ ታሪክ ባለቤቶችና አናብስት ልጆች ዛሬ እየሆነ ያለውን ላስተዋለ በእውነትም እናሳዝናለን፡፡
በተሰለፉበት ግንባር አያሌ ኢትዮጵያውያን የጦር አበጋዞችና የሠራዊቱ አባላት ለሀገራቸው ክብር ታላቅ መስዋእትነት ከፍለው በአድዋ ጦር ሜዳ ወድቀዋል፡፡የጠላት ጦር መድፎች በተኩስ ኃይል ባስቸገሩም ግዜ ፊታውራሪ ገበየሁ ፊት ለፊት ደረታቸውን ሰጥተው በመሄድ የጠላትን መድፍ አውድመው መስዋእትነት ከፈሉ፡፡
ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ ተብሎ የተገጠመውም ያኔ ነው፡፡ ከድል በኋላ ከጦር ሜዳ የተመለሰው ሠራዊትና መሪዎች የክብር ሰላምታ እየሰጡ በንጉሠ ነገሥት እምዬ ምኒልክ ፊት ሲያልፉ የፊታውራሪ ገበየሁ ጦር ከፊታቸው ሲቃረብ የፊታውራሪ ገበየሁ ፈረስ ብቻውን ከፊት እየተጎተተ ሲሄድ ያዩት ምኒልክ የገበየሁን መሞት አወቁና ስቅስቅ ብለው አለቀሱ ይባላል፡፡እንዲህ ታላቅ የደም ዋጋ በእልፍ አእላፍ ጀግኖች የተከፈለላት የገዘፈ ታላቅ ታሪክ ሀገር ነች ኢትዮጵያ፡፡
ታላላቅ ስመ ጥር ኢትዮጵያውያን ጀግኖች የጦር መሪዎችና ሠራዊታቸው ከመላው ኢትዮጵያ ተውጣጥተው በአድዋ ጦር ሜዳ የዘመቱት ለሀገራቸው ክብርና ነጻነት ሲሉ ነው፡፡በዚህ ጦርነት የፋሽስት ኢጣሊያን ምርጥ የተባሉ አዋጊ ጄነራሎች ከነሠራዊታቸው ተማርከዋል፡፡ በአድዋ ጦርነት የኢጣሊያ ሠራዊት በጥቁር ሕዝብ መሬት በጥቁር ሕዝቦች ጀግንነትና ታላቅ ተጋድሎ የመሸነፉ ዜና በመላው አውሮፓ ሲሰማ ድንጋጤን ፈጠረ፡፡ ሚዲያዎቻቸው ይሄንኑ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ነጮች በጥቁሮች የመሸነፋቸውን ዜና የኢትዮጵያን ድል አድራጊነት በመላው አለም አሰራጩት፡፡
የነጮች የበላይነት በጥቁሮች የጦር ሜዳ የበላይነት የሽንፈት ጽዋውን ተጋተ፡፡በአፍሪካ መሬት ውስጥ በምትገኝ ኢትዮጵያ ተብላ በምትጠራ ሀገር ጥቁር ሕዝቦች በነጮች ላይ ከተቀዳጁት ድል በፊት በየትኛውም የአለም ክፍል በነጮች ላይ የተገኘ ድል አልነበረም፡፡
የኢትዮጵያ ድል በመላው አለም ለሚገኘው ጥቁር ሕዝብ ለነጻነቱ ተግቶ እንዲዋጋ ፈር ቀዳጅ ሆኖ በር ከፈተ፡፡የታላቁ ንጉሠ ነገሥት አጤ ምኒልክና የባለቤታቸው የእቴጌ ጣይቱ ስም በመላው አለም አስተጋባ፡፡ይህ ድል በኢትዮጵያውያን ጀግኖች በአድዋ መሬት ላይ በታላቅ መስዋእትነት ባይገኝ ኖሮ ሌላ ሊመክታቸውና ድል ሊያደርጋቸው የሚችል ኃይል አልነበረም፡፡ ለዚህም ነው በዘመኑ ገጣሚው ምኒሊክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ግዜ አበሻ ሲል የገጠመው፡፡
የዚህ ድል ባለቤቶች ከመላው ኢትዮጵያ ከሰሜን ከመሀል ከደቡብ ከምእራብ ከምስራቅ በየጦር አዝማቾቻቸው አማካኝነት የዘመቱት የኢትዮጵያ ጀግኖች ናቸው፡፡ትግራይ አድዋ ድረስ ለወራት ተጉዘው የዘመቱትና ተዋግተው ድል ያደረጉት የኢትዮጵያ ጀግኖች ታሪክ በጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ ገዝፎና ደምቆ የሚታይ ተምሳሌነቱን በመውሰድ በቅኝ ግዛት ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች ለነጻነታቸው ለመዋጋት ቆርጠው የተነሱበት በአፍሪካ ለፓን አፍሪካ መመስረት መሰረት የጣለበት ታላቅ ታሪክ ነው፡፡
የማይበገረውና የማይታጠፈው የኢትዮጵ ያውን የጸና አንድነት ለሀገራቸው የነበራቸው ጥልቅና እስከመስዋእትነት የዘለቀ ሞት አይፈሬ ቁርጠኝነት ነው በዛን ዘመን እጅግ ዘመናዊ የተባለውንና ከኢጣሊያ በመርከብ ተጉዞ ምጽዋ ተራግፎ ትግራይ ተጓጉዞ አድዋ ላይ የመሸገውን የፋሽስት ሠራዊት ፊት ለፊት ገጥሞ በመበታተን ድል ያደረገው፡፡ይህ ታላቅ ድል በመላው ጥቁር አለም በአውራነት ሲታወስ የሚኖር ድልና ገድል ነው፡፡
ይህ ድል የኢትዮጵያውያን የጸና እና የማይፈረካከስ አንድነት ጥልቅ የሀገር ፍቅር ስሜት ታላቅ ጀግንነት ያስገኘው ሕብር ውጤት ነው፡፡ የዘመኑ ኢትዮጵያዊ ትውልድ በቅድመ አያቶቹና በአባቶቹ በእናቶቹ ኃያል ተጋድሎና ጀግንነት መኩራት ብቻ ሳይሆን ምንግዜም የሀገሩን አንድነትና ክብር ለመጠበቅ ምሳሌነታቸውንም አጥብቆ ሊከተል ይገባዋል፡፡ ሊከፋፍሉት ሊበታትኑት የሚከጅሉትን የታሪክ ውርዴዎች ጸንቶ በመታገል አባቶቹ በታላቅ ተጋድሎና መስዋእትነት ያቆዩዋትን ሀገር በዘርና በጎሳ ሳይከፋፈል እርስ በእርስም ሳይባላ የውጭ ኃይሎች የሚሸርቡትን ሴራ በመበጣጠስ አንድነቱን ሕብረቱን ጠብቆ ሀገሩን ማልማትና ማሳደግ ታሪካዊና ትውልዳዊ ኃላፊነቱ መሆኑን በውል ሊገነዘበው ይገባል፡፡
የዛሬው የትውልዱ ጦርነት ከድህነትና ከኋላቀርነት ጋር ነው፡፡ አንድነቱን አጽንቶ በመቆም በአሸናፊነትም በመውጣት ታላቅ ታሪክ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ክብርና ሞገስ ነጻነታችንን በታላቅ ተጋድሎ አስጠበቀው ላቆዩን አያት ቅደመ አያቶቻችን አባቶቻችንና እናቶቻችን ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ይሁን፡፡በአንድነታችን ጸንተን ስንቆም ሀገራችንን ኃያልና ገናና እናደርጋታለን፡፡ክብራቸውን ነጻነታቸውን ሀገራቸውን ከልብ የሚወዱት የሞት አይፈሬዎቹ እናት የሆነችው ኢትዮጵያ ለዘለአለም ትኑር !!

 

መሐመድ አማን

Published in ኢኮኖሚ

የዓድዋ ድል ታሪክ በማናቸውም ዓለም ያሉ ዘጋቢዎች፣ የታሪክ ጸሀፍቶች፤ የጥበብ ባለሙያዎች ማናቸውም ገድሉን ለመተረክ ለሚፈልጉ ሰዎች በየትኛውም መንገድ ለመፃፍ ምቹ ነው፡፡ ለአፃፃፍ ነጻነትን ይሰጣል፡፡ በዓለም ላይ ለነፃነት፣ ለአልሸነፍ ባይነት፣ ለአገር ወዳድነትና ለዘላለማዊ ክብር መራራ ፅዋን መጎንጨትን ለወሰኑ ዜጎች ክብር ሲሆን፤ ግን ደግሞ የተከፈለበት መስዋዕትነት ሲወሳ ዓድዋ የታሪክ ሁሉ ቁንጮ ይሆናል፡፡ 

አድዋ በኃይል ሚዛን ያልተመጣጠነ ጦርነት ተካሂዶ ያልተጠበቀ ውጤት የተመዘገበበት ነው ፡፡ በተለይም ደግሞ ድል ለተጠሙና የነገን ፍካት ለሚናፍቁ ህዝቦች ከዓድዋ ድል በላይ የሚጠቀስ የጽናት ተምሳሌት ከቶውንም ሊኖር አይችልም፡፡
ታዲያ ይህንን እውነት የተገነዘቡ በርካታ ግለሰቦች፣ ተቋማት፣ ደራሲያን፤የታሪክ ምሁራን፣ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮችና ባለሙያዎች ዓድዋን በተለያዩ ወቅቶች በማይደበዝዝ ቀለማት ከትበው አልፈዋል፤ አሁንም እየከተቡ ናቸው፡፡ነገም የሚነገርለት አኩሪ ታሪክ ነው ፡፡
በርካታ ሚሊዮን ተከታዮች ያሉት እና ስሙ በዓለም የናኘው አማዞን ዶት ኮም የተባለው ድረገጽም ስለ ዓድዋ ድል መደበቅ አልተቻለውም፡፡ እንዲህም ሲል ይተርከዋል ‹‹ዓድዋ አፍሪካውያን ከባርነት ቀንበር አፈንግጠው እንዲወጡ የጥርጊያ መንገድ ያመቻቸላቸው ነው፡፡ይህ ድል ቀድሞ የነበረውን አውድ በእጅጉ የለወጠና ታሪክ መልኩን እንዲቀየር ያደረገ ትዕይንት ነበር፡፡ ድሉ የጣሊያንንም አቅል ያሳተ እና ለኢትዮጵያውያን እጥፍ ድርብ የኩራት ካባ ያላበሰ ነው ››ሲል አስቀምጧል፡፡
ኒው አፍሪካን ኒውስ የተሰኘው ድረገጽም ስለ ዓድዋ በሰፊው በገለጸው ትንታኔው ለነገሮች ሁሉ የፀብ መነሻ ሆነው አንቀጽ 17 እንደነበር በሰፊው አትቷል፡፡ እናም ከዚያን ጀምሮ ኢትዮጵያ እና ጣሊያን የጎሪጥ መተያየት መጀመራቸውንና ውሎ አድሮ ደግሞ ደም መቃባቱ አይቀሬ እንደሆነ የሚያሳዩ በርካታ ምልክቶች መታየታቸውን ይተነትናል፡፡ ለዚህ ሁሉ መነሻ ደግሞ እብሪት የወጠረው የወቅቱ ያጣሊያን መንግሥት ሲሆን፤ የውጫሌው ስምምነት አንቀጽ 17 ለጦርነቱ መቀስቀስ ትልቁና አወዛጋቢው አጀንዳ እንደነበር ነው የሚያወሳው፡፡
በ19ኛው ክፍለዘመን ብዙዎች የአፍሪካ አገራት በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ላይ ስምምነት አድርገው አፍሪካን መቀራመት ጀምረው ነበር፤ አደረጉትም፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን በኢትዮጵያ ላይ በተደጋጋሚ የተቃጣው ሙከራ ሳይሳካ ቀረ፡፡ ጣሊያኖችም ከቀይ ባህር ወዲህ ዘልቀው ኢትዮጵያን መግዛት ተሳናቸው፡፡
በዚህም የተነሳ ጣሊያኖች ደም ጠማቸው፡፡አጼ ምኒልክ ደማቸው ፈላና በባዶ እግራቸው ጥርሳቸውን ነክሰው ጦርነት ለመግጠም እንደወሰኑ ነው የሚያብራራው፡፡ ከአፍሪካ አገራት አኳያም ሲታይ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በመፅሐፍት ውስጥ ያላት ታሪክ ሌላ ነው፤ እናም ሌሎች የአፍሪካ አገራት ቅኝ ተገዝተው እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ይሁንና ይህ የተሸናፊዎች ምዕራፍ በኢትዮጵያውያን ሳይደገም በዓድዋ ሌላ ታሪክ ተሠራ፡፡ ይሁንና አይናቸውን ከኢትዮጵያ ላይ ሳይነቅሉ ቅኝ የመግዛት ፍላጎታቸው እና ምኞታቸው ህሊናቸውን አውሮት ቢቆይም ከምኞት የዘለለ አልነበረም ይላል፡፡
አፍሪካውያን ከዓድዋ ድል በታሪክ ምን ሊማሩ ይችሉ ሲል ይጠይቃል የመረጃ ምንጩ፤ እንዲህም ሲል ወደ ሰፊ ትንታኔው ይዘልቃል፡፡ ምንሊክ እና ህዝባቸው ለአገራቸው በእጅጉ ታማኝ የሆኑበት እና ለዓላማቸው በጽናት የተዋደቁ ናቸው፡፡ ጠላትንም ደፍረው ከገጠሙት ድባቅ መምታት እንደሚቻል የታየበት ነው የዓድዋ ድል፡፡
አጼ ምነልክ መጀመሪያ ያደረጉት ነገር ቢኖር በአገር ውስጥ ከተለያዩ ገዥዎች ጋር ያላቸውን አጀንዳ ትተውት ልዩነቱን አስወገድው የጋራ ጠላት ላይ ለመረባረብ ወሰኑ፡፡ በዚህም ከተስማሙ በኋላ በአራቱም ማዕዘናት 100ሺ ወታደሮችን በአንድ ላይ አሰባሰቡ ይላል፡፡ ወደ ዓድዋ የሚደረገው ጉዞ እየሰመረ መሄዱንና የጀግንነት ወኔ መቀጣጠሉን ይተነትናል፡፡
ስለእውነት ከሆነ አፍሪካውያን ከዓድዋ ድል የሚቀስሙት ትልቅ ትምህርት አለ ሲል ይተነትናል፡፡ በተለይም ደግሞ ጠላትን በጋራ ሆኖ ማደባየት እና ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ይነገራል፡፡ በዚህ ጦርነት ወቅት ራስ መኮንን፣ ራስ ተክለሃይማኖት፣ ራስ መንገሻ ዮሐንስ ከትግራይ፤ ራስ ሚካኤልን ከወሎ፣ ራስ ወሌ ከየጁ ኦሮሞ፣ እንዲሁም በጦርነቱ ወቅት የተሰውት ራስ ገበየሁ ተከታዮቻቸውን በማዝመት እና ለአገራቸው ክብር በመዋደቅ የማይተካ የተጋድሎ ሚና ነበራቸው፡፡ኃያላን የሆኑትን በህብረት ማሸነፍ እንደሚቻል ያስተማረ ነው ዓድዋ፡፡ የኢትዮጵያ ገዥ የነበሩት አጼ ምኒልክ በውቅቱ ከእርሳቸው ጋር የስልጣን ሽኩቻ ውስጥ ገብተው የነበሩ አመፆኞችን እንኳን ሳይቀር ለአገራቸው እንዲዋደቁ ያሰለፉ ጀግና ነበሩ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ከምኒልክ ጎን በመሆን ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱም የጦርነቱን ማርሽ ቀያሪ እንደነበሩ እና ሴቶችም ለአገራቸው ክብር ዝቅ ብለው ለትውልድ ቀና የሚያደርግ ታሪክ እንዲያስቀምጡ ያስቻለ ናቸው፡፡ እቴጌ ጣይቱ ከምኒልክ ጎን በመሆን የጦር አውድማው በወኔ የተሞላ እንዲሆን አድርገው እንደነበር ያስታውሳቸዋል፡፡ በዚህም ለበርካታ እንስቶች ተምሳሌትና ሚስት ለባሏ እውነተኛ ረዳት እንደሆነች የታየበት ነበር፡፡ ጣይቱ በጀግንነት ለአገር ክብር የምትዋደቅ ፊት አውራሪ መሆኗን ተርኮላታል፡፡በዚህ ጦርነት ድሉ በአንድ አካል ብቻ የተገኘ ባለመሆኑ አፍሪካውያን ከዚህ ትብብርን ሊማሩ ይችላሉ ሲል ይቋጫል፡፡
«አፍሪካን ለማወቅ መጀመሪያ ኢትዮጵያን እወቁ» ሲል ሀተታውን የሚጀምረው ብላክ ፖስት ኦርግ ደግሞ የታሪክ ቁንጮ የሆነውን የዓድዋን ድል ለመስበክ የተጠቀመበት ርዕስ ነው፡፡ በጥቁሮች ታሪክ ላይ በሚያጠነጥነው ድረገጽ ያሰፈረው ጽሁፍ ጥንታዊት አብሲኒያና ጣሊያን እ.ኤ.አ 1896 ከፍተኛ ትግል በገጠሙ ጊዜ ለአገራቸው ነፃነት የታገሉት ድል ተቀዳጁ፤ጠላትን የዶግ አመድ አደረጉት፡፡ በማለት የዓድዋን ድል በደም የተዋጀ እና ታላቅ እንደሆነ ይመሰክራል ጹሁፉ፡፡ አውሮፓውያኑ ለራሳቸው መደላድል ሲሉ ‹‹አፍሪካን መቀራመት›› በሚል ኀሳብ የጀመሩት ውጥንም ተሳክቶላቸው፤ ከኢትዮጵያ ምድር ሲደርሱ ግን ህልማቸው ከሸፈ ይላል፤ በወቅቱ ስለተደረገው ተጋድሎ እና አኩሪ ድል ሲያብራራ፡፡ የዓድዋ ጦርነት ከፖለቲካዊ ፋይዳው በዘለለ ግለሰባዊ ስሜትና አንድምታው ትልቅ አንደሆነ ይነገራል፡፡
የአገር መሪዎች በአድናቆት የሚናገሩለት የዓድዋ ታሪክ እንዲህ ይገለፃል፡- የቀድሞ የደቡብ የአፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ የዓድዋ ድል አፍሪካውያንን በርካታ ዕድሎች የፈጠረና ወራሪን ማሸነፍ እንደሚቻል ያሳየ ታሪካዊ ድርጊት እንደሆነ ነበር በአንድ ወቅት የተናገሩት፡፡ በርካታ ጥቁር ህዝቦች አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲራመዱ ሁኔታዎችን ያመቻቸ እንደነበርና ይህም ዘላለም ሲወሳ እንደሚኖር ነው የሚተርኩት፡፡
ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት፤ በወቅቱ የነበሩ ራስ ገዞች ከምኒልክ ጋር ያላቸውን ልዩነት ትተው በአገራቸው ጉዳይ ላይ ማተኮራቸውን በማስታወስ አፍሪካውያን ይህንን እንደ ትምህርት ሊወስዱ ይገባል፡፡ምኒልክ ያላቸውን መሳሪያ በአግባቡ እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ያውቁ ነበር፡፡ ከዚያም አለፍ ሲል መልካም ወዳጆች አፍርተው ነበር፡፡ በታቻላቸው መጠንም የራሳቸውን በዘመናዊ መሳሪያ ለመጠቀም እና ለማምረት የሞከሩ ናቸው፡፡ በወቅቱ የሰለጠኑ ወታደሮች ሳይሆኑ አገራዊ ወኔያቸው የገፋፋቸው ጀግኖች ነበሩ፡፡ ከጦርነቱ ጀርባ ሁሉም ድርሻ ነበረው፡፡ አርሶ አደሩ ከኋላ ስንቅ ያቀብላል፤ ወታደሩም ይጠናከራል በዚህ ሂደት ነው ኢትዮጵያ ጣልያንን ማሸነፍ የቻለችው፡፡

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

 

Published in ዓለም አቀፍ

ምዕራባውያኑ አፍሪካን እንደ ቅርጫ ሥጋ ለመቀራመት በጀርመን በርሊን ከተማ ተማምለው ሲያበቁ ኢትዮጵያ በጣሊያን እጅ እንድትወድቅ ተፈረደባት፡፡ ጀግኖች አባቶቻችን ግን ዓድዋ ትፍረደን አሉ፡፡ የውጫሌ ስምምነት ይሏት አንቀፅ 17 እሳት አስጫረች፤ ጦር አማዘዘች በኢትዮጵያውያንና ጣሊያን መካከል 1888 ዓ.ም፡፡
በዚያን ወቅት ኢትዮጵያውያን ጦርና ጎራዴ ይዘው ለዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች እንግዳ የነበሩ አያቶቻችን፤ ከታንከኛና ከመድፈኛ ጋር ጦርነት የገጠሙ እጆች የሰማይ በራሪ አውሮፕላኖችን እያዳሸቁ እንኩትኩት ሲያደርጓቸው ዓለምን ጉድ አስብለው አፋቸውን አስያዙ፡፡ ፀሀፍትም ታሪኩ መራራ ቢሆንም ሊከትቡት ከብዕር ተናነቁ፡፡
የዓድዋ ድል ጦርነት ዝምብሎ ጦርነትን አሸነፈ ተብሎ የሚፃፍ፤ የሚዘከር አልነበረም፡፡ አንዲት ጠብታ ውሃ፤ ሰደድ እሳትን ከምድረ ገጽ እንዳጠፋች የሚነጻፀር እንጂ፡፡ በዓድዋ ጦርነት ወቅት በርካታ የክፍለ አገር ገዥዎች እኔ እገዛ እኔ እገዛ በሚል ጦር ተማዝዘው ጠዋትና ማታ እርስ በእርስ ይጠዛጠዙ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይሁንና ጠላት በመጣ ጊዜ የፖለቲካ ሽኩቻ አላገዳቸውም፤ የሃይማኖት ልዩነት አልታያቸውም፤የፆታ ነገር አልገደ ባቸውም፡፡ ሁሉም እምነቱ፤ ሃይማኖቱ፤ ሚስቱ፤ ርስቱ፤ ማንነቱ ሁሉ አገር ነበር፡፡ ማን በአገር ይደራደራል፡፡
አብዛኞቹ ጦርነቱ ሲጀመር ነገሩ የዳዊት እና ጎልድ ጨዋታ ይሆናል ብለው ገምተው ነበር፡፡ እንደ ነዲድ እንጨት ለእሳት ተማግደው፤ ‹‹ማን ያሸንፈኛል›› ብሎ ከፊታቸው ተሰልፎ የነበረውን የጠላት ጦር አብረከረኩት፡፡ ስንት ሕይወት ገብረው፤ በስንት መከራ ተፈትነው ይኸው ነፃ ትውልድ ተፈጠረ፡፡ አይ ጀግንነት፤ አይ ወኔ!
የዓድዋ ድልን ለኢትዮጵያውያን ሲያወሩት የሚያምር ለጠላት ግን እንኳንስ ሊያወሩት ቀርቶ ሲያስቡት መራር ነው፡፡ የዓድዋ ድል በእርግጥ ዘላለማዊ ድል ነው፡፡ የማይደበዝዝ፤ ፍትህ ለተጠሙ የሚያበረታታ የማይጎመዝዝ የፅናት ተምሳሌት ነው፡፡ ስለ ዓድዋ ዘላለም ቢጻፍ ቢተረክ የማያሰለች ከክፍለ ዘመን በፊት በጎልያድ እና ዳዊት መካከል የተካሄደ የጦርነት አምሳል ነው፡፡
በጦርነት ወቅት ንጉሠ ነገሥት ኢትዮጵያ አፄ ምንሊክ ጠላት በአገራቸው በመጣ ጊዜ ክብሬ፤ ማዕረጌ አላሉም፡፡ በሃሳብ የማይስማሟቸውን ሰዎች አላራቁም፡፡ በአገር ጉዳይ የጋራ ጠላት መጥቶብናል እና ኑ! አገራችንን ከወራሪ እናድናት ብለው ነበር ነጋሪት የጎሰሙት፡፡
የዓድዋ ድል ማለት ልዩ ክስተት ነው፡፡ በመሞት ውስጥ የኖረ ሕይወት ነው፡፡ የዓድዋ ድል ማለት በማይነገር ረቂቅ ትዕይንት ውስጥ በሚጣፍጡ ቃላት፤ አፍ በሚያስከፍት ድርሰት ተከሽኖ ጀግኖች የሚግባቡበት ቅቡል ቋንቋ ነው፡፡ ዓድዋ ማለት ለጨለመባት አፍሪካ የብርሃን ወጋገን ያሳየ ማለት ነው፡፡ ብቻ ዓድዋ! ማለት ከኢትዮጵያውያን በስተቀር ለቀሪው የዓለም ህዝብ ህልም የሚመስል ግን የተጨበጠ እውነት ነው፡፡ በቃ ዓድዋ ብዙ ነው!
በዚያን ወቅት የሮምን አደባባይ አስቧት፡፡ በሀዘን ማቅ ተውጣለች፡፡ በዚያን ወቅት አስቡት በዓድዋ ለአገራቸው ክብር መስዋዕት የሆኑ አባቶችና እናቶች አስከሬን ተረፍርፏል፤ ግን የጀግና አስከሬን! እንኳንስ በሕይወት ኖረው ሞተው የሚያርበደብዱ የሀበሻ ጀግኖች!
አባቶቻችን ለትናንት ማንነታቸው ሲጨነቁ የዛሬ ማንነታችንን አቆዩልን፡፡ የትናንት ታሪክን ላለማጉደፍ ሲዋደቁ፤ የእኛን ዛሬ ታሪክ አደመቁት፤ ለዛ አበጁለት፡፡
ዓድዋ ላይ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ደማቸውን አፍስሰው ነው ዛሬ የምንኖርባትን ምድር ያስረከቡን፡፡ የምንግባባበትን ቋንቋ፤ የምንጽፍበትን ፊደል፤ የምንቀኝበትን ዜማ፤ ያቆዩልን፤ ከባዕዳን ባህልና ቋንቋ የታደጉን በትዕግስትና በብልሃት እንጂ በለው፤ በለው! አሳድደው በሚል መርህ አይደለም፡፡
ወጣቱ ከቀደምት አባቶች አንዳች ነገር ሊማር ግድ ይለዋል፡፡ በዚህ ዘመን ጦርነት የለም፡፡ ፌዴራላዊ ሥርዓት ተዘርግቶ ብዙሃንን ጨፍልቆ የሚኖርበት እድል የተመናመነ ይመስለኛል፡፡ አባቶቻችን ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው አገርን ሊገነባ በሚችል አጀንዳ ላይ እንዴት እንደተጠመዱና ስምና ዝናቸውን አስከብረው እኛንም አስከብረው የኖሩ ስለመሆናቸው ማጤን ይገባል፡፡
ታዲያ ይህ ለዛሬው ትውልድ ዕዳ ነው፡፡ ወራሪን ከአገር ለማስወጣት በአንድነት ያበረ ክንድ በአሁኑ ወቅት የተገላቢጦሽ ሆኖ አንዱን ሰው ከሌላ ክልል የመጣህ ነው ብሎ ማሳደዱ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ሆኗል፡፡ ለመሆኑ ይህ ምን ይሉት ፈሊጥ ነው? አንዱ ያፈራውን ንብረት ሌላው እያወደመ አገሬ ብሎ ማቀንቀን ከወዴት የመጣ ፈሊጥ ነው? ታዲያ! ከ122 ዓመት በፊት የነበረ ንቃተ ህሊና ዛሬ ላይ ወደዬት ተሰወረ? እንኳንስ ለኢትዮጵያውያን ቀርቶ ለሚሊዮኖች የአፍሪካ ወንድምና እህቶች አርዓያ የሆ ነች አገር ስለምን ውጥንቅጦች ውስጥ እየገባች መጣች ብለን መጠየቅ ይገ ባል፡፡
እንደ ቅጠል ረግፈው ያቆዩልንን አገር እንደ ቄጠማ አለምልመን ማስቀጠል እንጂ ጊዜው እንዳለፈበት የባህር ዛፍ ቅጠል ከመሬት ላይ መወ ርወር የለብንም፡፡ ያሻገሩንን ባህር አል ፈን፤ ትንሽዋ ኩሬ አስምጣን እንዳታ ስቀረን ሁላችንም በንቃት ማየት አለ ብን፡፡
በእኔ እምነት ይህ ትውልድ በዓድዋ ድል ብቻ የመጣ ከፍሎ የማይጨርሰው ዕዳ አለበት፡፡ በዚያን ዘመን አንድነቱን አጠናክሮ ጠላቱን ያልፈለሰፈ ህዝብ ዛሬ እንደምን ድህነትን ማሸነፍ ይሳነዋል፤ እንዴት በባዶ እጁ በዓለም ጦረኛ የተባለን ሰራዊት ድባቅ የመታ ህዝብ የእለት ጉርስ ይቸግረዋል? እነዚያ አባቶቻችን ዛሬ ቀና ብለው ቢያዩን ምንኛ ባዘኑብን፤ ምንኛ በተቀየሙን! አፅማቸው ይወቅሰናል፡፡
በነገራችን ላይ የዓለም ታሪክ የአሸና ፊዎች ናት፡፡ ዓድዋ ላይ አሸን ፈናል፡፡ ግን ደግሞ አሁን ተሸንፈናል፤ ቁጭት ርቆናል፤ እልክ እና መነሳሳት ያንሰናል፡፡ በጉንጭ አልፋ ክርክሮች ተጠ ምደናል፡፡ ነገን ብሩህ ከማድረግ በዘለለ ትናንት ላይ ተጥደናል፡፡ ዓድዋን መድገም እንዴት ይሳነናል? ይህን ግን መለወጥ ግድ ይለናል፡፡ ሁላችንም በተመደብንበት ሞያና ኃላፊነት ላይ በአግባቡ ከሠራን ሁሌም ዓድዋ አለ፤ ከምንምነት ወደ ስልጣኔ ማማ ከወጣን ሁሌም ድል አለ፡፡
እኛ ለዚች ዓለም ህዝብ በውድ ዋጋ መሸጥ ከምንችለው ትልቁ ሃብታችን አንዱ የዓድዋ ድል ነው፡፡ ማንም ሰው ቢመጣ ‹‹ኮፒ ራይቱ›› የእኛ ብቻ የሆነ ነው የዓድዋ ድል፡፡ የዓድዋ ድል ብንሸጠው የማያልቅ ሃብታችን ነው፡፡ እናማ ኑ! እንሽጠው፡፡ ዓድዋን እናስ ተዋውቅ፡፡ ስለ ዓድዋ በተናገርን ቁጥር አልሸነፍባይነት ስነልቦናን በትውልድ ልብ ውስጥ ማኖር ነውና፤ በወጣቱ ልብ ውስጥ አይበገሬነትን ማንገስና ታሪካችንን መና ገራችን ነውና፡፡ የዓድዋን ድል ስንሸጠው ስንለውጠው ብንውል አይሰለችም፤ ምክንያቱም ውድ፤ ብርቅና ድንቅ ነው፡፡ የጠንካራ ስነልቦና ተምሳሌትና የማይ ንበረከኩ አልሞ ተኳሽ አባቶቹን ጀብድና ገድላቸውን ማን አልሰማ ይላልና! ዓድዋን እንዘክረው፤ እናስተዋውቀው፤ እንማ ርበት፡፡
ስለዓድዋ ድል ከተናገርነውና ብዙዎች ከተናገሩት፤ የታሪክ ድርሳናት ፍንትው አድርገው ከፃፉትና ከፃፍነው ሁሉ ገና ያልተነገረ፤ ገና ያልተጻፈ አለ፡፡ ወዲህ ደግሞ ይህን ታሪክ የሚያኮስስ ድህነት የሚባል ደንቃራ ከፊታችን ተገትሯል፡፡ እናም ታሪካችን ሙሉ ይሆን ዘንድ ዛሬም ነገም መትጋት አለብን፡፡
ዛሬ እየሞትን ሳይሆን እየኖርን ታሪክ መስራት የምንችልባቸው አጋጣ ሚዎች በርካቶች በመሆናቸው ሁላችንም ኃላፊነ ታችን ልንወጣ ይገባል፡፡ በትናንት ታሪክ ብቻ የምንኩራራ ህዝቦች ሳንሆን፤ ከትናንት ታሪክ የሚቀጥል ሌላ የታሪክ ምዕራፍ መክፈት ይገባናል፤ ግዴታችንም ነው፤ እርሱም ድህነትን ታግሎ ማሸነፍ፡፡ የሆነው ሆኖ ግን በ21ኛው ክፍለዘመን ውስጥ ሆነን እንደ 19ኛው ክፍለ ዘመን ማሰብ ግድ ባይለንም ታሪክን መዘንጋት ግን አይገባም፡፡ በዚያን ዘመን ግፍ እና ሰቆቃ ያደረሱብንን ሰዎች አንርሳቸው፤ ቂም ግን አንያዝባቸው፡፡

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

Published in አጀንዳ

በኢትዮጵያና በጣሊያን መካከል በዓድዋ የተካሄደው ፍልሚያ በታሪክ ውስጥ ከፍተኛውን ስፍራ ያለው በዓለምአቀፍ ደረጃ ትኩረትን የሳበና ለአፍሪካውያን ከፍተኛ መነቃቃትን ያላበሰ የታሪክ ነፀብራቅ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ለወረራ ምክንያት ትፈልግ የነበረችው ጣልያን ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛቷ ሥር ለማድረግ መንገድ ይከፍትልኛል ብላ ያሰበችውን የውጫሌ ውል ከአፄ ምኒልክ ጋር በጣሊያን ተወካይ ኮውንት ፔትሮ አንቶኔሊ በኩል ብትዋዋልም የውሉ የአማርኛና የጣልያንኛው ትርጉም ለየቅል የነበረው 17ኛው አንቀፅ ተቀባይነት ማጣቱ ለጣልያን መንግሥት የክብር ጉዳይ ሆኖ ክብሩን ለማስጠበቅ ጦርነት እስከመክፈት እንደሚደርስ ፎከረ፡፡
ያኔ እቴጌ ጣይቱ ‹‹የዛሬ ሳምንት አድርገው፡፡ እኔ ሴት ነኝ፡፡ ጦርነት አልወድም፡፡ ነገር ግን አገሬ እንደዚህ ያለ ክብርን የሚነካ ዘለፋ ከምትሸከም ጦርነትን እመርጣለሁ፡፡ ሂድ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ፡፡ እግሩን ለጠጠር ደረቱን ለጦር ሰጥቶ፣ ደሙን ለአገሩ ፍቅር አፍስሶ፣ እሱ ወድቆ አገሩን የማያቆም እዚህ ያለ እንዳይመስልህ፡፡ ሂድ የኢትዮጵያን ሰው ባታውቀው ነው፡፡ ለአገሩ መሞት ማለት ለሐበሻ ጌጡ ነው፡፡ ሂድ ባሻህ ጊዜ ተመለስ ተሰናድተን እንጠብቅሃለን፡፡ ያንተን ወንድነትና የጣይቱን ሴትነትም ያን ጊዜ እናየዋለን፤ ሂድ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ፤›› በማለት ለዓድዋ ጦርነት የክተት ጥሪ ያህል ቦታ የሚሰጠው ታሪካዊ ንግግር ማድረጋቸውን ታሪክ ያስታውሰናል፡፡
የዓድዋ ድል በዓለም ታሪክ አውሮጳውያን አፍሪካን ለመቀራመት ተስማምተው በቅኝ ግዛት ሲከፋፈሉ ክፉ ድርጊታቸው አፍሪካውያንን አንገታቸውን እንዲደፉ አድርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ለነፃነታቸውና ለአገራቸው ዳር ድንበር መከበር ኢትዮጵያውያን ተጋድሎ አድርገው ድል በመቀዳጀታቸው መላው የአፍሪካ ጥቁር ህዝቦች ካቀረቀሩበት ቀና ብለው ነፃነትን እንዲያስቡ ብርሃን ፈንጥቋል፡፡
ይህንን ድል ተከትሎ በተለያዩ አፍሪካዊ ቅኝ ተገዢ አገራት የፀረ ቅኝ ግዛት ንቅናቄዎችና የነፃነት ፋኖዎች ሊፈጠሩ ችለዋል፡፡ ኢትዮጵያም በዚህ የዓድዋ ድል ምክንያት የመላ አፍሪካውያን ኩራትና ተስፋ ለመሆን በቅታለች፡፡ ድሉ የአውሮፓ የቅኝ ግዛት ናፋቂዎችን በአፍሪካውያን ላይ ያላቸውን ከንቀት የሚመነጭ አስተሳሰብ ቆም ብለው እንዲፈትሹ አስገድዷቸዋል፡፡
በአንድ ወቅት የቀድሞው የኩባ መሪ ፊደል ካስትሮ ከተለያዩ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ተቋማት ለተወጣጡ ጋዜጠኞች መግለጫ እየሰጡ ባሉበት ወቅት አንዲት ጣልያናዊት ጋዜጠኛ«በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል በነበረው ጦርነት የኩባ መንግሥት ለኢትዮጵያ ያደረገው ድጋፍ ሶማሊያ እንድትሸነፍ አስተዋፅዎ አድርጓል» ስትል ለሰነዘረችው ሃሳብ ካስትሮ« ስለኢትዮጵያውያን ጀግንነት አያቶችሽን ጠይቂ!» ሲሉ ነበር የኢትዮጵያን አርበኞች ጀግንነት አያቶቿ ዓድዋ ላይ ከተከናነቡት ሽንፈት እንድትማር ያመላከቷት፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን እንዲህ የሚዘከርለትና የሚነገርለት የዓድዋ ድል ባለቤቶች ነን፡፡አፄ ምኒልክና የጦር አበጋዞቻቸው፣ የዚያ ዘመን ጀግኖች አባቶቻችን ክብርና ሞገስ ይግባቸውና ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው የታፈረችና የተከበረች አገር አስረክበውናል፡፡
እኛ የዚህ ዘመን ትውልዶች የወረስነው እንዲህ ያለ ታላቅና ደማቅ ታሪክ ምንያህል ከባድ አደራ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ወጣቱ ትውልድ በአገሪቱ በተፈጠረው ሰላምና በተጀመረው የልማት ሥራ ተሳታፊ በመሆን ቀፍድዶ ከያዘን ድህነት ለመላቀቅ ብርቱ ጥረት ማድረግ ይገባዋል ፡፡ዛሬ በዓለም ያሉ አገራት ጠላቶቻቸው በሸረቡላቸው ሴራ ተጠልፈው እርስ በርሳቸው እየተናቆሩ ሰላም እርቋቸው ፣በደህና ጊዜ የገነቡዋቸውን የልማት ሥራዎች በጦርነት አጥተው፣ ለስደት ተዳርገውና የሚቀምሱት አጥተው ማየት ምንኛ ያሳዝናል?
እኛ ኢትዮጵያውያን ችግር ከደረሰባቸው ተምረን ሰላማችንን ለመጠበቅ አፍራሾችን በሩቁ በመከላከል አገራችንን ለማልማት ቀሪ የቤት ስራዎቻችን እየሰራን በዓድዋ የተገኘውን አኩሪ ድል በልማት የላቀ ውጤት በማስመዝገብ መድገም ይኖርብናል፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

ውጫሌ፡- ለአድዋ ጦርነት መነሻ ምክንያት የሆነው የውጫሌ ውል የተፈረመበትና ይስማ ንጉሥ በመባል የሚታወቀውን አካባቢ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን የአምባሰል ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ ፀሐይ ወሌ እንደተናገሩት፤ ሙዚየምና ሎጅን ጨምሮ ስምምነቱን የሚዘክሩ ማስታወሻዎችን ለመገንባት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቅቀዋል፡፡ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በመደበው 25 ሚሊዮን ብር ሙዚየምና ሎጅ ለመገንባት ካሸነፈው የአማራ ህንጻ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ጋር ርክክብ ተፈጽሟል፡፡ ግንባታውንም በሦስት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅና በቀጣይ የውጫሌን ውል የሚያስታውስ ሐውልት ለመገንባት የዲዛይንና የታሪክ ጥናት ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው፡፡
ታሪካዊ የውጫሌ ውል የተፈጸመበት ይስማ ንጉሥ ታሪኩ በሚገባ ሳይታወቅና የቱሪዝም መዳረሻ ሳይሆን በርካታ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በዚህም የአካባቢው ህብረተሰብ ከቱሪዝም ዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ ህብረተሰቡ በቦታው ላይ ስምምነቱን የሚዘክሩ ማስታወሻዎች እንዲገነቡ በተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረቡን አስታውሰው፤ የእርሻ መሬቱን ከመስጠት ጀምሮ ሥራው እንዲሳካ ሁለገብ አስተዋፅኦና ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ተናግረዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ዲዛይነር አቶ ሳሙኤል አባተ፤ ሐውልቱን ጨምሮ ሌሎች ግንባታዎችን ለማከናወን 80ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተናግረው፤ በአሁኑ ወቅት የክልሉ መንግሥት በመደበው 25 ሚሊዮን ብር ግንባታውን ለማከናወን የሚያስችሉ የግብዓት ማሟላትና የማቅረብ ተግባራት መከናወናቸውን፤ የክልሉ መንግሥትና የአካባቢው ማህበረሰብም ፕሮጀክቱን ለማሳካት እያደረጉት ያለው ርብርብ ተስፋ ሰጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአድዋ ድል የመላው አፍሪካዊን ድልና ኩራት በመሆኑ ሁሉም የአፍሪካ አገራት ለፕሮጀክቱ መሳካት ድጋፍ እንዲያደርጉ አቶ ሳሙኤል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ለአድዋ ጦርነት መነሻ ምክንያት የሆነው የውጫሌ ውል ሚያዝያ 25 ቀን 1881ዓ.ም ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክና በኢጣሊያን ተወካይ ኮውንት ፔትሮ አንቶኔሊ መካከል በአምባሰል ወረዳ ይስማ ንጉሥ በተባለ ቦታ የተፈረመ ስምምነት መሆኑ ይታወሳል፡፡

አንተነህ ቸሬ

Published in የሀገር ውስጥ

አድዋ፡- የአድዋ ድል ታሪካዊ ቦታዎችን የማስተዋወቅና የማልማት ዓላማ ያለው የአድዋ ተራሮች እና የአድዋ ጦርነት ድል ቱሪዝም ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ ፡፡
የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ እንደገለፁት፣ በመንግሥት የመነሻ ገንዘብና ከባለድርሻ አካላት በሚደረግ ድጋፍ የሚከናወነው ፕሮጀክቱ፣ ታሪካዊውን የአድዋ ድል በማስተዋወቅና በማልማት ረገድ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ከመንግሥት በተጨማሪ ሌሎች አካላትም በስፋት የሚሳተፉበት ፕሮጀክቱ፤ በዓይነቱና በዓላማው ለየት ያለ እንደሆነ ገልፀዋል። የአድዋ ድል ታሪክ የመላው ጥቁር ህዝብ ድልና ኩራት በመሆኑ ሁሉም አካላት ለፕሮጀክቱ መሳካት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአክሱም ዩኒቨርሲቲ መምህርና የፕሮጀክቱ ኃላፊ የሆኑት አቶ ተክለብርሃን ለገሠ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ የሀውልትና የመካነ መቃብር ግንባታዎችን ጨምሮ ሌሎች ተያያዥ ግንባታዎችን ያጠቃልላል፡፡በሦስት ዓመታት ጊዜያት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው ፕሮጀክት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ያጎላዋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ለፕሮጀክቱ ግንባታ የሚያስፈልገው 260ሚሊዮን ብር በመንግሥትና በተለያዩ ተቋማት ይሸፈናል ተብሎ እንደታቀደ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

አንተነህ ቸሬ

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።