Items filtered by date: Saturday, 03 March 2018

የባህል ፌስቲቫል ዋና ዓላማው ይሄው ነው። ባህልን ማሳወቅ የሌሎችን ባህል ማወቅ። ኢትዮጵያ ያሏት ባህሎች ተደጋግሞ የተባለለት ነው። ይህንኑ ድንቅ ባህሎቿን ነው በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ እያሳየች ያለችው። በዚህ ዓመትም አንድ ዓለም አቀፍ የባህል ፌስቲቫል ላይ ተሳትፋለች። እንዲ ያውም በፌስቲቫሉ ላይ ልዩና ትኩረት የሳበች ሆና እንደ ነበር የፌስቲቫሉ ተሳታፊዎች ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የባህል ቡድን አስተባባሪ እና የሙዚቃ ተጫዋች የሆኑት አቶ ደረጀ ተክሉ እንደሚሉት፤ የባህል ፌስቲቫሉ ‹‹አስዋን ኢንተርናሽናል ፌስቲቫል›› የሚባል ሲሆን፤ ያዘጋጀውም የግብጽ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ነው። ዝግጅቱም አስዋን ላይ ተደርጓል። በፌስቲቫሉ ላይ ከተለያዩ የዓለም አገራት የተውጣጡ የባህል ቡድኖች ተሳትፈውበታል።
በአስዋን ከተማ ውስጥ በሚገኝ «አምፊ ቴአትር» የየአገራቱ የባህል ቡድን ትርኢት ለአምስት አምስት ደቂቃ ለመክፈቻ ያህል ማሳየት ጀመረ። ከዚያ በኋላ በመድረኮች፣ በጎዳናዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በገበያ አካባቢዎች፣ ህዝብ በሚሰባሰብባቸው ቦታዎች ላይ ትርዒቱ ቀጠለ። በአስዋን ግድብ አካባቢ ባሉ መርከቦችና ጀልባዎች ላይም ትርዒት ታይቷል። የየአገሩ የባህል ሙዚቃ ቡድን መርከብ ላይ እየወጣ ያሳይ ነበር። የሚቀርበው ትርዒት ሁሉ በአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን እንደነበረውም አቶ ደረጀ ያስረዳሉ።
በፌስቲቫሉ ላይ የኢትዮጵያ የባህል መዚቃ ቡድን የክብር እንግዳ ነበር፤ ጥሩ አቀባበል ተደርጎለታል። የኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ ቡድን ያቀረበው ትርዒት የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። ለዚህም ብዙ የሽልማት ስጦታዎችን አግኝቷል። የተሰጡ ግብረ መልሶችም ከፍተኛ አድናቆት የነበራቸው ናቸው። የኢትዮጵያ ባህልም ሆነ የባህል ሙዚቃ የብዙዎችን ቀልብ የሳበው ከሌሎች የዓለም አገራት ልዩ መልክ ስላለው እንደሆነ አቶ ደረጀ ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ባህልም ሆነ የባህል ሙዚቃ አፍሪካ ውስጥ ካሉ አገራት እንኳን ይለያል። ብዙ አገራት በባህል፣ በሙዚቃ፣ በድምጽ ይመሳሰላሉ፤ የኢትዮጵያ ግን የተለየ ነው። የድምጽ ቅላጼው፣ አጨፋፈሩ ሁሉ ልዩ ነበር። ይህ ደግሞ የብዙዎችን ቀልብ እንዲስብ አድርጎታል። በኪነ ጥበብ ውስጥ ቀልብን የሚስበው ወጣ ያለ ነገር ነው። ከተለመደውና ደጋግሞ ከሚታየው ነገር የተለየ ሲሆን ተመልካቹ ትኩረት ይሰጠዋል። በዚህም የኢትዮጵያ ባህልና ሙዚቃ እንደሌሎቹ አገራት ከውጭው ጋር ተመሳሳይነት ያለው አይደለም፤ የራሱ ቀለምና የራሱ ድምጸት(ቶን) ያለው ስለሆነ ትኩረት እንደተሰጠው አቶ ደረጀ ይናገራሉ።
አቶ ደረጀ በግብጽ የባህልና የቅርስ አያያዝ በጣም እንደተደነቁ ይናገራሉ። ያላቸውን ቅርስ ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ፣ «ቴምፕል» የተባለውን ቅርሳቸውን ለማስተዋወቅ ዝግጅት የሚያደርጉት እዚያ ነው። ቴምፕል ለግብፆች የሥልጣኔያቸው መነሻ ነው። የአስዋን ግድብ ሲሞላና ሲጎድል የሚያውቁት ውሃው ቴምፕሉን በሚውጠው መጠን ነበር። በኋላም በቴክኖሎጂ ከውሃው ውስጥ አውጥተው ከአካባቢው አስቀመጡት። እንዲህ አይነት ዝግጅቶች ሲኖሩ ግን የሚያደርጉት ቴምፕሉ ጋ ሲሆን፤ የባህል ሙዚቃ ፌስቲቫል መዝጊያም የተደረገው እዚያው ነበር። ያላቸውን ቅርስ ዓለም አቀፍ ሥርጭት ውስጥ እንዲገባ የሚያደርጉት ጥረት ለኢትዮጵያ ትልቅ ትምህርት እንደሆነ ተረድተዋል።
«የባህል ሙዚቃ ቡድኑም ከግብጽ የተማረው ቅርስንና ባህልን እንዴት ማስተዋወቅ እንደሚቻል ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ታሪካዊ ቅርሶች አሉ፤ ዳሩ ግን የሚገባቸውን ክብካቤ ያገኙ አይደሉም። በዓለም አይን ውስጥ ለማስገባት የሚደረገው ጥረት አናሳ ነው። ግብጾች ባህላቸውን ሲያሳዩ ከታሪካዊ ቅርሶቻቸው ጋር አያይዘው ነበር። ዝግጅቱን እዚያ ያደረጉበት ምክንያትም ለዚሁ ነው። ከተለያዩ የዓለም አገራት የመጣው ቡድን ይመለከትላቸዋል። በተጨማሪ ግልጽነት ለመፍጠር ሲሉ በመብራትና በተለያየ ገላጭ ስክሪኖች ያስወቡታል» በማለት አቶ ደረጄ ካዩት ነገር ብዙ ትምህርቶችን እንዳገኙ ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ ቡድን በግብጽ ከነበረው ቆይታ አንድ ነገር ግልጽ ሆኖለታል። የኢትዮጵያ ባህል በውጭው ዓለም ትኩረት መሳብ እንደሚችል፤ እንደተባለውም እንደሌሎች የዓለም አገራት በባህልም ሆነ በሙዚቃ ተመሳሳይነት እንደሌለው በዚህም ማንም በቀላሉ ሊለየው እንደሚችል ነው። ይህ ደግሞ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ እንዲህ አይነት የባህል ቡድን በብዛት መኖር እንዳለበት ያምናሉ።
ይህ ካልሆነ ግን በአለባበስም ይሁን በአጨፋፈር የውጭውን ለመምሰል የሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያዊነት ውበቱን ያሳጣዋል። የምዕራቡን ዓለም ፋሽን ይዘን የምንገኝ ከሆነ ማን ሊያየን ይችላል? ኢትዮጵያን ሊጎበኝ የመጣም የራሱን አገር ፋሽን ይዘን ከጠብቅነው ምን የተለየ ነገር ሊያገኝ ይችላል?በሌላ በኩል ከግብጾች የታሪክና ቅርስ አያያዝም የባህል ቡድኑ እንደነገረን ብዙ ነገር መማር እንችላለን።
ለአብነትም በግብጽ ማንኛውም የማህበረሰብ ክፍል ታሪኩን በሚገባ እንዲረዳ የተለያዩ ዝግጅቶችን ሲያደርግ ሊታወቅ በሚገባው ቦታ ላይ መሆኑ ሁሉም ታሪኩን ያውቃል። በእኛ አገር ግን አሁን አሁን ትልልቅ የታሪክ ቦታዎችን ‹‹እኔ አላውቅም›› የሚል ወጣት እየተፈጠረ ነው። እናም ከግብጾች ይህንን መማር ይገባናል። ለወጣቱ ትውልድ ማሳወቅም የሁሉም ድርሻ መሆን እንዳለበት አቶ ደረጀ ያስረዳሉ።

ዋለልኝ አየለ

Published in ማህበራዊ

«ሰው...ሰው ነው» ይሏል! እናሳ ሰውማ ሰው ነው'ንጂ ሌላ ምን ይሆናል? የሰውን ሰውነት ዝቅ በማድረግ የናቁ ከፍ በማድረግም የታበዩ ነጮች በአንድ ጥቁር ሰው፤ በአንዲት ታላቅ አገር መሪ ንቅናቄ ንቃት አገኙ። የሰው ሰውነት ከሰው ዝቅ ይላል። የሰውም ሰውነት ከሰው ከፍ ይላል ብለው አንገታቸውን የደፉ ጥቁር ሕዝቦች ቀና ለማለት የእውነትን ምክንያት ተሸለሙ። አድዋ የዚህ ሁሉ ማሠሪያ ሆነ!
ወደኋላ እንመለስ፤ የፊልም ጥበብ ባለሙያዎች ምልሰት /flashback/ ይሉታል። የአድዋ ድል ካለፈ ሰባት ዓመታት ተቆጥረዋል። እምዬ ምኒልክ የአድዋ ድል ምንም እንኳ ለጥቁር ሕዝብ ጭምር ድል ቢሆንም የሰው ልጆች ህይወት ተቀጥፏልና ሀዘንም እንደሚገባ ለሕዝባቸው ተናገሩ። የሰው ልጅ ክቡር ነውና! ይህንንም ሰለጠንን ከሚሉት ይልቅ የአሸናፊዎች ልብ ያውቀው ነበር።
በዛም ጊዜ እንዲህ ሆነ፤ በፊታቸውም አስቀድሞ የሆነውን ነገር በትርዒት ለማሳየት ባለሙያዎች ተሰየሙ። በንጉሱ ፊት ከሰባት ዓመቱ መታሰቢያ ቀድሞ የሆነው ነገር ሁሉ ደግሞ በምልሰት ቀረበ፤ ክተት ተጠርቶ አገሬው ሸክፎና ተደራጅቶ ሲወጣ። ከንጉሱ ጋር ቅያሜ ቢኖረው እንኳ «ንጉስ ቢሄድ ንጉስ ይተካል፤ አገር ቢሄድ አገር አይተካም» ብሎ ጀግና ጦሩን ሰብቆ ሲዘምት፤ «ጦር ሜዳን የወንድ ያደረገው ማን ነው? ደሜን አፈስላታለሁ የምትላት አገር የእኔስ አይደለች?» ብላ ለውጊያ ከወንድሟ ጋር ብርቱ ሴት ስትወጣ፤ ከጠላት ፊት ለፊት የተናነቀ ቆራጥ ህይወቱ ሲሰዋ፤ የብዙዎች ታሪክ በአንድ የድል መዝገብ ላይ ሰፈረ።
በአምባላጌ ጦርነት ድሉ የኢትዮጵያ ሆነ። ተሸናፊዎች ግን መሸነፋቸውንም ሆነ ከተማረኩ በኋላ በይቅርታ ሂዱ መባላቸውን ሊቀበሉ አልፈቀዱም፤ ሊያምኑም አልቻሉ። ንጉሱ ደግሞ የተማረኩት ሁሉ ቢወድዱ ኢትዮጵያን አገሬ ብለው እንዲቀመጡ ካልፈለጉም ወደአገራቸው እንዲሄዱ አሰናበቱ። አቅምና ኃይል ያለው ፍቅርና ይቅርታንም የራሱ ገንዘብ እንዲያደርግ እኚህ ታላቅ መሪ በፍቅር ይቅርታን አደረጉ። ከድል የበለጠ ድል እነሆ!
አምባላጌ እና መቀሌ ላይ ሽንፈት ያልጠገበው የጣልያን ጦር ግን ኃይሉን አጠናክሮ ቀጠለ፤ አድዋ! ፉከራና ሽለላው፤ ቀረርቶና የእረኛው ዜማ እንኳን አገሬ ላለ የጠላትንም ልብ ወዲህ ያስሸፍታል። የእኔ ላላት አገር ማን ወደኋላ ይላል? ታድያ እነዚህ ሰዎች ሊሸለሙ እንጂ መች ሊዋጉ የሚሄዱ ይመስላሉ? ፉከራና ሽለላቸውን አይቶና ሰምቶ ያሸነፉ እንጂ ገና ድላቸውን ያልተቀበሉ የሚላቸው ማን ነው? ማሸነፍ ከድል ሲቀድም እንዲህ ይሆን?
«...የስጋ ሞት አይደለ፤ የስም ሞት ይጎረብጣል!» አለች ገጣሚዋ ትዕግስት ማሞ፤ የአገራቸውን ስም አስቀድመው፤ የአገራቸውን ክብር ከፍ አድርገው፤ ከሰው በላይ ነን ያሉትን ሰዎች ልካቸውን አሳይዋቸው፤ በአድዋ። ሰው ከሰው እኩል መሆኑን ዓለም በዚህ ድል መስታወትነት ተመለከተ። «የሰውነት ማህተም ቀለም...ከአገራቱ አልፎ ለዓለም» አሉት፤ አድዋን።
በንጉሱ ፊት የቀረበው ትርዒት አበቃ። ወዲህ እንመለስ፤ ከምልሰቱ ወጥተን ወዲህ ወዳለንበት ጊዜ። የአድዋ ድል 122ኛ ዓመት ወደሚከበርበት ዓመት፤ 2010ዓ.ም። ትርዒቱ በጣይቱ ሆቴል ግቢ ውስጥ የቀረበ እንደሆነም ልጠቁማችሁ። አዘጋጆቹ «የሙዝየም ቴአትር» ብለውታል። ታዳምያን ታሪኩ በኪነጥበባዊ መንገድ በሚቀርብበት ስፍራ ሆነው በታሪኩ ውስጥ የነበሩ ያህል እንዲሰማቸው የማድረግ አቅም ያለው የቲያትር ዘውግ ነው።
አርባ ለሚጠጋ ደቂቃ የቆየው ይህ ቴአትር እጅግ በርካታ ተዋንያንን ያሳተፈ ነው። ሚዩዚክ ሜይዴይን ጨምሮ ፍላጎት ያላቸው ወጣቶችንና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴአትር ተማሪዎችን አሳትፏል። የግቢው ጥበት ታዳሚውን አላስጨነቀም፤ የስፍራው አነስተኛ መሆን ተዋንያኑን አልገደበም። ይልቁንም የታሪኩን መቼት ለማድመቅና የተለያየ ታሪክን በአንድ ላይ ለማሳየት ተጠቅመውበታል።
ቴአትሩ በሁለት መሠረቶች ላይ ቆሟል። ዋናው ታሪክ የአድዋ ድል ሆኖ በምልሰት ከ115 ዓመታት በፊት፤ የአድዋ ድል ባለፈ በሰባተኛው ዓመት ላይ የሆነውን ያስታውሳል። ሁለተኛ ደግሞ ለጦርነቱ ጥሪ ከተደረገ ጀምሮ እስከአድዋ ድል ድረስ የሆነውን ነገር በንጉሱ ፊት በትርዒት መልክ የሚያስቃኝ ነው። በዚህም ታዳሚው ከንጉሱ ጎን እንዳሉት ካህናት፣ መኳንንት እና ባለሟሎች የሆነ ያህል እንዲሰማውና አብሮ የድሉን ታሪክ እንዲመለከት ሆኗል።
ከዛም አልፎ ከታዳሚው መካከል የቴአትሩ አካል የሆኑ ሰዎች መኖራቸው የበለጠ ቴአትሩ ታዳሚውን ባይተዋርነት እንዳይሰማው ያደረገ ነው። የጣልያን ጦር እንዳ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን መሽጎ እንደሚገኝ በታወቀ ጊዜ፤ ደግሞም ኢትዮጵያ ወደአምላኳ እየተለማመነች፤ «ያድኅነነ እመዓቱ...ይሰውረነ በምኅረቱ...በእንተ ማርያም ወላዲቱ» ስትል በአራራይ ዜማ፤ ዜማውን አጉልቶ የተቀበለ ከታዳሚው መካከል የወጣ ድምጽ ነው። ይህም ታዳሚው ሳይቀር እንዲሳተፍ የሚጋብዝ ነበር።
ከታሪኩ በተጓዳኝ የሰውን ትኩረት የሚስበው የፉከራና ሽለላው ክፍል ነው። ተዋንያኑ ወኔ በተመላበት መልኩ የሚያደርጉት ፉከራ እና ሽለላ ትወና ነው ለማለት ከቴአትሩ መውጣትን ይጠይቃል። ታሪኩ የገባቸው፣ የተሰጣቸው ገጸባህሪ የተዋሃዳቸውና የተላበሱት እንደነበሩ በእርግጥ ያስታውቃል። በዜማ በኩል ከዋሽንትና ከጥሩንባ እንዲሁም ከመለከት የሚወጡት ድምጾች ከፉከራው፣ ከሽለላውና ከእልልታው ጋር ተባብረው አድዋ ላይ በትክክል በምልሰት የሚወስዱ ናቸው። «ያኔም እንዲህ ነበር ለካ!» ያሰኛሉ። በታሪክ ከምናውቀው የእኛው ጀግንነት ተካፋይ ያደርጋል፤ ነጻነት ከተገዛበት ድል እንደመ ቃመስ!
በቴአትሩ መካከል ላይ ሶስት ገጣምያን ከታሪኩ ጋር የሚሄዱ ግጥሞችን አቅርበዋል። ኅብረ ዝማሬዎችም በመሐል ገብተዋል። ከትዕይንቶቹ መካከል አንዳንዱ በታዳሚው ፊት እየታየ በትረካ የታጀበ መሆኑ ደግሞ ቴአትሩ በብዙ መንገድ የተሰናዳ መሆኑን ያሳያል። በጥቅሉ ቴአትሩ ትልቁን ታሪክ እጥር ምጥን አድርጎ ነው ያቀረበው ማለት ይቻላል። በዛም ውስጥ የብዙዎችን ታሪክ አስቃኝቷል። ይህ ግን የታሪክ ፍሰቱን አንዳች ቦታ ላይ ሲረብሸው አይታይም።
ትዕይንቶችም ከአንዱ ወደሌላው ያለምንም እንከን ተቀባብለውታል። በዚህ ሁሉ ጥንካሬ ውስጥ ታድያ ቢስተካከሉ የሚባሉ ነገሮች አይጠፉም። የቴአትር አንዱ አቅም የተዋንያኑ ድምጽ እንደመሆኑ መጠን ጎልተው የማይሰሙ ድምጾች ነበሩ። እነዚህ ድምጾች አንድና ሁለት ደቂቃ ለማይሞላ ጊዜ የቆዩ መሆናቸው በቀላሉ እንዲታለፉ አድርጓል። የአዘጋጆቹና የአስተባ ባሪዎቹ ቅልጥፍና እና ትርዒቱን በጥሞና እየተከታተሉ መምራት ግን በሚገባ ታይቷል።
ፉከራና ሽለላው ላይ የተገኙ እና ከተዋጊዎች መካከል የሆኑቱ በአለባበሳቸው ኢትዮጵያን የሚያሳዩ ነበሩ። በአንጻሩ የጣልያን ሠራዊትን ሆነው የተወኑት የቀረቡት በተመሳሳይ ጥቁር ልብስ ነው። ይህም የልብስ ምርጫ ባለሙያው ሌላ ሊያስተላልፈው የፈለገው መልዕክት ከሌለ፤ ለምሳሌ ጥቁር እንደጠላት የሚታይ በመሆኑ ጣልያንን በዛ መልክ ሊስል የፈለገ ካልሆነ በቀር ሌላ አማራጭ ቢኖር የተሻለ ይሆን ነበር። እነዚህ ነገሮች ልብ ቢባሉ መልካም ነው አልን እንጂ አንዳች ያጎደሉ እንዳልሆኑ ግን ልብ ይሏል!
ወደማጠቃለሉ ነን፤ መቼም ለምዶብን አልያም ደንብ ሆኖ ሊዘመርላቸው ለሚገባን የምንዘምረው ጊዜው ሲደርስ ወይም «ቀኑ ነው» ብለን በሰየምነው ጊዜ ነው። እንደ አድዋ ያለ ትልቅ ድል እድሜ ዘመናችንን ሙሉ አገራችንም እስካለች ድረስ አብሮን የሚቆይ ቢሆንም የተለየ ትኩረት የሚያገኘው የካቲት 23 ሰሞን ነው። መገናኛ ብዙኅን፣ ግለሰቦች፣ ድርጅቶች፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ብቻ ሁሉም በየመስኩ ይዘምራል፤ አድዋ! አድዋ! አድዋ! ይላል!
«አድዋ የሰው ልጅ ማህተም ነው፤ ከሰው በላይ ወይም ከሰው በታች የሚባል ሰው እንደሌለ ዓለም የተረዳበት» ይላል፤ ሰውኛ ፕሮዳክሽን «ክብር አድዋ» ብሎ በሚንቀሳቀስበት ሥራው። ክብር አድዋ የጎዳና ላይ ትርዒትን ጨምሮ የአድዋን በዓል በሚመለከት የተለያዩ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶችን አካቷል። ይህ ቴአትር ደግሞ ከዝግጅቶቹ መካከል አንዱ ነው።
ጥበብ ሰዎችን እርስ በእርስ የማስተሳሰርና የማግባባት ኃይል አላት። ያም ብቻ አይደለ ክውን ጥበብ የቀደመውን ትውልድ ከዛሬው ጋር ከእውን በሚማሰል ምናብ ታጋምዳለች። እንዲህ ያለ ኃይል ያለውን ክውን ጥበብ፤ በቴአትር መልክ ያየነውና ከላይ እንዳለው በዝርዝር ያቀረብነው ባለፈው ሐሙስ የካቲት 22 ቀን 2010 ዓ.ም በጣይቱ ሆቴል የተመለከትነውን ነው።
ቴአትሩ ብዙ ዘመንን በቅጽበት የመኖር ያህል እንዲሰማ ያደርግ ነበር። የአገር ባህል ልብስ የለበሱና የቀደመው ዘመን የሚመስሉ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ተዋንያንና ወጣቶች በቁጥር ብቻ ሳይሆን በግርማ ሞገስ ጊቢውን ሙሉ አድርገውታል። ኩነቱን በመቅረጽ ለማቆየት ባለሙያዎቹ ሲሯሯጡ ነበር። በጥበብ የአገር ነገር እንዲህ ስሜትን ከቀሰቀሰና የታሪኩ ተጋሪ ለመሆን ታዳሚውም እንዲያ የተደሰተ፤ ያኔ ተፈጥረን ቢሆንስ ኖሮ የኢትዮጵያዊነት ወኔ ማንን ቤቱ ያስቀምጠው ነበር? ቴአትሩ እንዲህም እንድናስብ ያደርጋል። ሰላም!

ሊድያ ተስፋዬ

Published in ማህበራዊ
Saturday, 03 March 2018 23:44

የአዋጁ ፋይዳዎች

ከየካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም አርብ ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዛሬ 17ኛ ቀኑን ይዟል። ፋይዳዎቹና ያስገኛቸው በረከቶችም ቀላል አይደሉም። ባለፉት 17 ቀናት ያገኘነውን እፎይታ እናውቀዋለን። ምስክር አያስፈልገንም። ለብዙኃኑ ህዝብ አንድ ቀን እንኳ በሰላም ውሎ ማደርና ወጥቶ መግባት «ልጄን ምን አግኝቶት ይሆን?» ከሚል ስጋት መገላገል ትልቅ ፀጋ ነው። ተመስገን ማለት መቻል በራሱ ተመስጌን የሚያሰኝ ነው።
የሩቁን እንጃ እንጂ አዲስ አበባ ግን ከአዋጁ ወዲህ የተረጋጋች ከተማ ሆናለች። በየታክሲው ማቆሚያውና በየአውቶቡስ ማዞሪያ አምስትና ሰባት እየሆኑ በቡድን ቆሞ ማሽካካትና በተለይ ከክልል የመጡ ወጣቶች በነዋሪው ሴት ልጆች ላይ የሚፈጽሙት ለከፋ ለከት አግኝቷል። አደብ ገዝቷል። ከጥቂት /ሁለት/ ዓመት ወዲህ ጀምሮ የቤቱ ጣሪያ እስኪበረቀስ ድረስ የነበረው እስክስታ መብረቅ ማባሪያ የሌለው ከርዳዳ የወጣቶች ጩኸት ደርዝ እየያዘ መጥቷል። አጠገብ ለአጠገብ የተቀመጡ ሦስት ወጣቶች ወዲህ ማዶና ወዲያ ማዶ እንዳለ የገጠር ገበሬ «ኧረ አያ እገሌ ውው...» ብሎ የሚጣራ ይመስል ላንቃቸው እስኪላቀቅ መጮህ ስልጣኔ መስሏቸዋል። ማይምነትና ኋላቀርነት መሆኑን የሚነግርልን አጥተን ነበር። እድሜ ለአዋጁ ምድረ ቦዘኔ ሁሉ አደብ ይዟል። እንደ እውነቱ ከሆነ የአዋጁ አብዛኛው ክፍል ዘለዓለም መኖር ያለበት ነው። ለምሳሌ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን ማወክ በሚለው ሥር ያለው መንገድና ሀዲድ መዝጋት የሚለው ጊዜ የማይገድበው ነው፡፡ /በነገራችን ላይ ሀዲድ ማለት አረብኛ ነው ብረት ማለት ነው ቁርአኑ ውስጥም አለ። «... ወአንዘልና ሀዲድ ፊሂ በዕሠ ሸዲደን ወመናፊዑ ሊናሲ» ይላል። ለሰው ልጅ ብዙ ጠቀሜታ ያለውን ጠንካራ /ሸዲድ/ ብረት /ሀዲድ/ ከሰማይ አወረድንላችሁ ማለቱ ነው። ሱራ ሐዲድ 57፡25/
በዚሁ ርዕስ ስር «ከተቀመጠው ታሪፍ በላይ መጨመርና የተከለከለ ስምሪት ማድረግ ተከልክሏል። እልልና እፎይ የሚያሰኝ ነው የትራንስፖርት ታሪፍ /ዋጋ/ መጨመርና ህዝብን ማስመረር አይቻልም። በድንጋይ ውርወራ ያልተሳካውን ህገወጥ ድርጊት በታሪፍ ጭማሪ በኩል ማሳካት አይቻልም። የተከለከለ ስምሪት ማድረግም መንገድን ማቆራረጥን የሚጨምር ነው። ህጋዊው ታፔላ «ከፒያሳ በመድኃኒዓለም ቀጨኔ» እያለ እነሱ ግን ከፒያሳ መድኃኒዓለም በአቋራጭ በማለት ከፒያሳ በ3ኛ ፖሊስ ጣቢያ በኩል ታጥፎ ውስጥ ውስጡን ሄዶ በችሎት አድርጐ መድኃኒዓለም ብቅ ማለት ነው። በዚህ ጉዞ እነ ሰሜን ሆቴል፣ ኢዜአ /ሾላ/ ፣ዘበኛ ሰፈር ይዘለላሉ። ከፍተኛ ህገወጥነት ነው። ዋጋው /ታሪፉም/ ቢሆን ከፒያሳ ቀጨኔ 2 ብር ከ75 ተወስኖ እያለ ታክሲዎቹ ከፒያሳ መድኃኒ ዓለም 3 ብር፤ ከመድኃኒዓለም ቀጨኔ ድረስ ደግሞ አንድ ብር ከሃምሳ ነው። በድምሩ የ2 ብር ከ75 መንገድ በ4 ብር ከሃምሳ ይኬዳል። የባሰ ሕገወጥነት ነው። አዋጁ ይህን ይከለክላል።
የሕዝብ አገልግሎት ማስተጓጐልን በተመለከተ የንግድ ሱቆችን መዝጋት ምርት ማቋረጥ ከሥራ ላይ መጥፋት ስራ ማቆም፣ አድማ ማድረግና ሥራን መበደል ተከልክሏል። ማንም እንደልቡ ሕዝብ ላይ የሚያላግጥበት ዕድል የለውም። ታዲያ ይሄ አሸወይና አይደለም? አንድ ኪሎ በርበሬ 40 ብር የነበረው በአንድ ጊዜ 150 ብር ሆነ ተባለ፤ ጉዳዩ ሲመረመር የነጋዴዎች አሻጥር ሆኖ በተደረገ ፍተሻም 177 ኩንታል በርበሬ ተደብቆ ተገኝቷል። በአዋጁ ምክንያት «ኑሮ ተወደደ» ለማሰኘትና ከእጥፍ እጥፍ በላይ ገንዘብ በአሻጥር ለማጋበስ በሚደረግ ደባ ሕዝብን ማስመረርና በመንግሥት ላይ ማስነሳት አይቻልም። ታዲያ ምን ያደርጋል የእኛ መንግሥት «ትዕግስት» በሚል ማስመሰያ ቃል የተሸፋፈነ ከፍተኛ ድክመትና ዝግመት አለበት። ለጥቂት ቀናት አስሮ በትንሽ ገንዘብ ዋስ ለቅቆ ያለተመጣጣኝ ቅጣት ይለቃቸዋል።
አንዳንዴ'ኮ በተለይ እንደበርበሬ ያሉ ምግብ ነክ ፍጆታዎችን ደብቆ በተገኘ ነጋዴ ላይ ምን እርምጃ እንደሚወስድና ችግሩን በዘላቂነት መፍታት እንዴት እንደሚቻል ካለፈው ሥርዓት ትምህርት መውሰድም መጥፎ አይደለም። ለአንድ ነጋዴ ጥቅም ሲባል መላውን ሕዝብ ማማረር ተቀባይነት የለውም። ከሕዝቡ ነፍስ ለነጋዴው ሕይወት ቅድሚያ የሚሰጥበትና የሚታዘንበት ሁኔታ ሊኖር አይገባም።
ሌላው የአዋጁ ፋይዳ በስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች የሚታይ አመጽና አድማ ማድረግ የተከለከለ መሆኑን መደንገጉ ነው። የስፖርት ሜዳ በተለይ እግር ኳስ መጫወቻ ሳይሆን መማቻ ሆኖብናል። ልጆቻችን ሞተውብናል ቆስለውብናል የድብድብ ሜዳ ሆኖብናል። እንኳን የታደሙት እኛም ገብተን የማናውቀው ጭምር በስጋት አልቀናል። መፍትሔ ይፈለግልን ብለናል። ወታደር ከገባበት ይባባሳል። በትምህርት ተቋማት አካባቢ ያለውም ሁኔታ ከአመጽና ከአድማ ነፃ እንዲሆን አዋጁ ያስገድዳል። ይህም ለእኛ ትልቅ እፎይታ ነው። ቢያንስ ልጆቻችን በሰላም ሲማሩ ውለው በሰላም እንደሚመለሱ እናስባለን። እነዚህ የእኛን የዕለት ተዕለት ሕይወት በቀጥታ የሚመለከቱ «ሰው ሰው» የሚሸቱ የአዋጁ ክፍሎች/ዝርዝሮች ናቸው። ሌሎቹ ሕገመንግሥቱንና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን የሚሉትና ሽብር፣ ጦር መሣሪያ፣ ትጥቅ ለ3ኛ ወገን ማቀበል /ማቀባበል/ ከኮማንድ ፖስቱ እውቅና ውጭ መግለጫ መስጠት፣... ቁም ሲሉ መቆም... ወዘተ የመሳሰሉት የፖለቲካ ነገሮች ናቸው። እንደአጠቃላይ ጉዳይ እንጂ ከሕዝብ ዕለታዊ ሕይወት ጋር በተዘዋዋሪ ካልሆነ በስተቀር የቀጥታ ግንኙነት የሌላቸው ቢሆኑም ለሀገር ሰላምና ልማት የግድ አስፈላጊ ፋይዳዎች ናቸው።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያስፈለገው ነገሮችን አለዝበን በሰላማዊና በመቻቻል ንግግርና በጋራ ለመፍታት ባጋጠሙ ችግሮች ምክንያት ነው፡፡ ኳሱን በእግራቸው ሥር አድርገው ሜዳ የገቡት የፖለቲካ ተጫዋቾች ነገሮችን አየር በአየር ከወዲያ ወዲህ ከመጠለዝ በቀር «ኳስ በመሬት» አድርገው ለመጫወት ባለመፈለጋቸው አጀንዳዎችን እየጠለዙ ፖለቲካውን አጦዙት። በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለማረጋጋት ከሚቻለው በላይ አደረጉት። አፀፋውም አዋጁ ሆነ። ከአቅም በላይ ሲሆንበት እንኳን መንግሥት ለስላሳው ድመት እንኳ ወደ አውሬነት ይቀየራል። ድመትን በር ዘግተህ መውጫ አሳጥተህ ብትቀጠቅጠው ነገሩ ከአቅም በላይ ሲሆንበት ለስላሳ የነበረው ፍጡር ወደ ነብርነት ተቀይሮ ሞነጫጭሮ ይጥልሃል። ምንም ድመት ቢሆን በዘሩ ነብር መሆኑን ያሳይሃል። «ኬሣ-ኬሣ አዱሬን ቢኒንሣ» ይላል ያገሬ ሰው።
ከመንግሥት ጋር ብቻ ሳይሆን እርስበርሳችንም በመካከላችን ያለው ግንኙነት በብልሃትና በኢትዮጵያዊነት ዘዴ ካልያዝነው ምላሹ አስከፊ ይሆናል። አንዱን ብሔር ለብቻ ነጥሎ በበላውና ባልበላው፤ በሆነውና ባልሆነው ምክንያት መውጫ መግቢያ አሳጥተን፤ በጥላቻ ዙሪያውን ከበን እንቀጥቅጥህ ብንለው የዚያ ብሔር ምላሽ እጅግ አስከፊ ሊሆን እንደሚችል ማሰብ አለብን። በዘዴ በመላ ካልያዝነው ነገር ይበላሻል። «የማን ቤት ጠፍቶ የማን ሊበጅ የአውሬ መፈንጫ ይሆናል እንጂ» ወደሚባል እልህና ቂም ሊያደርሰን ይችላል። አንዱን እናፈርሳለን ስንል ሁላችንም ተያይዘን እንጠፋለን።
ኢህአዴግንና ኢህአዴግ መራሹን መንግሥት የማንፈልግበት አንድ መቶ አንድ /101/ ምክንያቶችና / አብዛኞቹ ሰበቦች ናቸው/ ሊኖሩን ይችላል። የትኛውም ምክንያት ግን መንግሥትን በኃይል/ በግልበጣ/ ለመቀየር የሚያስችለን አይደለም።መንግሥትን በኃይል መወለጥ አይቻልም። ሕገመንግሥቱም አይፈቅድም። በዓለም ፊትም/ ዘንድም/ ተቀባይነት የለውም። የመንግሥትን ትዕግስት መስፋት እንደ ድክመትና እንዳበቃለት መቆጠር ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ሕገመንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማስከበር ያለበትን ኃላፊነት ለመወጣት እስከየ ትኛውም ጫፍ ድረስ ይሄዳል። ማንኛውንም ርምጃ ይወስዳል። መንግሥት ድንጋይ ተወረወረብኝ ብሎ እጁን ኪሱ ከትቶ ሥልጣኑን በትኖ መሄድ አይችልም። አገሪቱንና ሕዝቡን ለማንና የት ጥሎ ይሄዳል? የመንግሥት ጠላቶች ያሉትን ያህል የመንግሥት ደጋፊዎችም አሉ። ድምፃቸውን ሰጥተው የመረጡት አሉ። ቢሆንም ባይሆንም እሱው ይሻላል የሚሉ ሰላም ፈላጊ ሕዝቦች አሉ።
መንግሥትን መቀየር የሚቻለው በአመጽና በአድማ ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ በሆነ የምርጫ ሥርዓት ብቻ ነው። መሆንም ያለበት ይህ ነው። የሚያስፈልገን ሰላማዊ ሸግግር ነው። አርቆ መገመትና ማሰብ ያስፈልጋል። በእርግጥ የእኛ አገር ፖለቲካ እንኳንስ አርቆ ለመገመት አቅርቦ ለማየትም ያስቸግራል። ለምሳሌ ባሳለፍነው የአመጽና የአድማ ሰሞን የችግሩ መፍትሔ የአቶ ለማ መገርሳ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን እንደሆነ ተገምቶ ነበር።
አንድ ወዳጄ በሚያዘጋጀው ግሩም መጽሔት የፊት ሽፋን ገጽ ላይም ለማ መገርሳ በቀይ ምንጣፍ ላይ እየተራመደ ወደ ቤተመንግሥት ሲገባ የሚያሳይ ግሩም ድንቅ ፎቶ /በፎቶ ሾፕም ቢሆን / አድንቆና አሳምሮ ይዞልን ወጥቶ ነበር። በዚያ ምስል፡፡ «እንዲህማ ከሆነ አቶ ለማ ይንገሥ» አሰኝቶን ነበር። በመሐሉ ደግሞ አቶ ለማ የሙሴን ልብስ ለብሶና ያቺን ምትሃታዊ በትር/magic wand/ ይዞ ሁለት እጆቹን ዘርግቶ ባህሩን ለሁለት ሰንጥቆ እኛን ከፈርዖን መዳፍ አውጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲያሻግረን የሚያሳይ የፊት ሽፋን ያለው መጽሔት ወጣ። አሁን አረጋገጥን! ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ለማ መገርሳ መሆኑን አመንን! ይህ ከሆነ ሁለት ወር ሳይሞላው ለማን በቀይ ምንጣፍ ቤተመንግሥት ያስገባው መጽሔት በቁጥር 26 ዕትሙ ላይ ዶ/ር አብይ አህመድን ዙፋን ላይ አስቀምጦ በፊት ገጹ ይዞልን መጣ፡፡ አሁን አብይ ላይ ተቸክለናል። የመጽሔቶቹ አዘጋጆች ምንም ስህተት የለባቸውም። የፊተኛው የአገሪቱ ሙቀት የአቶ ለማ ነበር፤ የአሁኑ ሁኔታ ሙቀት ደግሞ ወደ ዶ/ር አብይ ተዛወረ። ትክክለኛውን ነው የዘገቡት። ችግሩ ያለው የእኛ ሀገር ፖለቲካ እንኳንስ የዓመት የአምስት ዓመቱን አሻግሮ ሊያሳየን ቀርቶ በወርና በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ እንኳ የሚሆነውን ነገር ለመገመት የማያስችል መሆኑ ላይ ነው።
በመሐል እኛ ለወሬ ፍጆታችን መነሻ የሚሆን ጊዜ ማሳለፊያ የጭቅጭቅ መድረክ አገኘን። ገሚሱ አባዱላን ሲል ከፊሉ ወርቅነህን ሲጠራ ከፊሉ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከኦሮሚያ አይሆንም ለምን ቢባል ፕሬዚዳንቱም ከኦሮሚያ/ ኦህዴድ/ ጠ/ሚኒስትሩም ኦህዴድ ሊሆኑ አይችሉም እያለ የራሱን ማብራሪያ ሲሰጥ ከረመ። የፕሬዚዳንትና በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ምርጫው በኢህአዴግ አቅራቢነትና በተወካዮች ምክር ቤት አጽዳቂነት ያውም በመደበኛ ሳይሆን በአስቸኳይ/ ድንገተኛ ስብሰባ/ ከሚወሰን በቀጥታ ተሳታፊነት በሕዝቡ ድምጽ በሚደረግ ምርጫ እንዲሆን የሚያስችል ሥርዓት ቢኖረንስ ያልን ዜጐችም አለን።
ለማንኛውም አሁን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ቀርቦ ፀድቋል።

ግርማ ለማ

Published in አጀንዳ

በአንድ ቀዝቃዛ ክረምት ወቅት ብዙ እንስሶች ሞቱ፡፡ ይሄን አስቸጋሪ ክስተት የተረዱት ጃርቶች አንድነት በመፍጠር ብርዱን ለመቋቋም ወሰኑ። በአንድ ላይ ተሰባስበው በመኖር እራሳቸውን ከብርዱ መከላከል ቻሉ፡፡ ነገር ግን ብዙ አልቆዩም። ትፍግፍግ ብለው በመሰባሰባቸው አንደኛው ካንደኛው ሙቀትን ማግኘት ቢችልም ያንዳቸው እሾሀማ ፀጉር የሌላኛውን አካል በማቁሰሉ መራራቅ እንደሚሻል በማመን ተበታተኑ። ይሁን አንጅ በመለያየታቸው ከመወጋጋታቸው የከፋ ለህልፈት የሚዳርግ የብርድ ቆፈን ነበር የጠበቃቸው።
ብርዱ እየጸናባቸው ሲሄድ ብልህነት የተሞላበትን ምርጫና ውሳኔ የሚፈልግ ሁለት አማራጭ ከፊታቸው እንደተደቀነ ተገነዘቡ፡፡ አንድም በእሾሃማ ፀጉራቸው አማካኝነት የተፈጠረውን ትንሽ ቁስል መታገስ ወይም ደግሞ በብርዱ ቆፈን እየተሰቃዩ አንድ ባንድ ከምድረ ገጽ መጥፋት፡፡ በዚህ ወሳኝ ሰአት ተረጋግተው ማሰብ ነበረባቸውና ሁሉም በየራሳቸው አሰቡ። አወጡ አወረዱና አንድ ስምምነት ላይ ደረሱ።
ጃርቶቹ እንደገና ወደ አንድነት በመምጣታቸው የሚፈጠረውን ትንሹን ቁስል ታግሰው ማሳለፍ እንዳለባቸው አመኑ። በአንድነታቸው የሚያገኙትን ትልቁን ጥቅም መርጠው ለትልቁ ጥቅም ትንሹን ችግር መታገስ ተገቢ እንደሆነ በማመናቸው ችግራቸውን በአንድነት ተጋፈጡት። በዚህ መንገድም አንድነትን ፈጠሩ፤ ሕይወታቸውንም ማቆየት ቻሉ፡፡
ሰዎች የሚኖራቸው የእርስ በርስ ግንኙነት በማናቸውም መንገድ ሙሉ ሊሆን አይችልም። አንድነት ለመመስረት ፍፁምነትን ከሰዎች መጠበቅ አይቻልም። እያንዳንዱ ሰው ያለውን ጉድለት በመሙላት ጥምረት መፍጠር እንደሚቻል ማመን ይገባል፡፡ በየትኛውም መስፈርት ሰዎች በአስተሳሰብ አንድ ሊሆኑ አይችሉም። በልዩነት ውስጥ ግን አንድነትን ማምጣት ይችላሉ። ልዩነትን መቀበል፣ ማክበርና መታገስ እስከቻሉ ድረስ አንድነትን መፍጠር ቀላል ይሆንላቸዋል፡፡ በጥምረትና በአንድነት የማይፈታ ችግር አይኖርም።
ጉዳዩን ወደሃገራችን ወቅታዊ ሁኔታ እናምጣው። ከዛሬ 122 ዓመት በፊት በ1888 ዓ.ም ጣሊያን በኢትዮጵያ ግዛት አዲግራት ላይ የመጀመሪያውን የቅኝ ግዛት ማስፋፊያ ዓላማ ያደረገ ወረራ አካሄደች። ንጉስ ምኒልክ ግን የአገራቸው መደፈር አንጀታቸውን ቢያሳርረውም ፈጥነው እርምጃ ለመውሰድ አልተነሳሱም። ምክንያቱ ደግሞ አቅማቸውን ማወቃቸው ነበር። የህዝባቸውን ሁኔታም መረዳት ነበረባቸው። ዓመቱን ሙሉ የጣልያን እንቅስቃሴ በንቃት እየተከታተሉ አቅማቸውን ማደራጀት ነበረባቸውና አደረጉት። በመቀጠል ለጦርነቱ ህዝቡን የክተት አዋጅ አሥነግረው ነጋሪት አስጎሰሙ። ከንጉሱ ጋር ቅያሜ ያላቸው ቢኖሩም እንኳ «ንጉስ ቢሄድ ንጉስ ይተካል፤ አገር ቢሄድ አገር አይተካም» በማለት ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ከ100 ሺ በላይ ገበሬዎች በአንድ ጥሪ ተሰባሰቡ።
የጥቁር ህዝብ በአውሮፓ ኃይል ላይ ድል ያደረገበት ሶሎዳ ተራራም የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ደማቅ ታሪክ በኢትዮጵያውያን ደም ተጻፈበት። በጦርነቱም ንጉስ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ፣ ራስ አሉላ፣ ራስ መኮንን፣ ራስ ሚካኤል፣ ራስ መንገሻ፣ ፊታውራሪ ገበየሁ፣ ደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ፣ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ እና በርካታ ጀግኖች በልዩነት ውስጥ በፈጠሩት አንድነት የማይፋቅ ታሪክ ለትውልድ አሥተላለፉ። ይህ ከሆነ ዛሬ 122 ዓመት አለፈው። ዛሬም ኢትዮጵያውያን ከውጭ የመጣ ወራሪ ጠላታችንን በአንድነት መክተን እንዳባረርነው ሁሉ የጋራ ጠላታችን የሆነውን ድህነትን ለማስወገድ መረባረብ ይኖርብናል።
ይህ ትውልድ ዛሬም ታሪክ እየሰራ ነው። «አድዋ በአብሮነት የአሸናፊነት ተምሳሌት» የሚል መሪ ሃሳብ የያዘው 122ኛው የአድዋ ድል በዓል ከዋዜማው ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል። የአባቶቹን አንፀባራቂ ታሪክ ተዳፍኖ እንዳይቀርና ተተኪው ትውልድ እንዲረከበው ለማድረግ በርካታ የታሪክ ማጋራት ስራዎች እየተሰሩ ነው።
በተለይም ወጣቱ ትውልድ 122ኛ የአድዋ ድል ከወትሮው በተለየ መልኩ ለማክበር ያደረገው ጥረት በኩራት ሊነገርለት የሚገባ ነው። ታሪክ ነጋሪ ብቻ ሳይሆን ታሪክ ሰሪም መሆኑን ያስመሰከረበት ወቅት ነው። የዘንድሮው የአድዋ ክብረ በዓል በአድዋ ሰንሰለታማ ተራሮች ሶሎዳ ተራራ ላይ በብሄራዊ ደረጃ በድምቀት ተከብሯል። በአፄ ምኒልክ ቤተመንግስት አንኮበር ላይ፤ እንዲሁም አዲስ አበባ አጼ ምኒልክ ሀውልት አካባቢ የተከበሩት ክዋኔዎች ላይ የወጣቶች ድርሻ ታሪክ የማይዘነጋውና በወርቃማ ቀለሙ ሊከትበው የሚገባ ሀቅ ነው።
ይህ ትውልድ የህይወት መስዋእትነት መክፈል አይጠበቅበትም። የሚጠበቅበት በሀገር ፍቅር ስሜት በደም የተፃፈውን የአድዋውን ታሪክ ማስጠበቅ ነው። ሀገሩ ከጠላት ታፍራና ተከብራ በመኖሯ የመኩራቱን ያህል ለመጭው ትውልድም ድህነትን ሳይሆን ብልፅግናን፤ መከፋፈልን ሳይሆን አንድነትን፤ ሁከትና ብጥብጥን ሳይሆን ሰላምን። በልዩነት ውስጥ የተሸመነ አንድነትን ሊያስተላልፍ ይገባዋል።
ከመግቢያችን ላይ እንደጠቀስነው ተረት አንድነት ህልውና መሆኑን ተረድቶ ያሉበትን ውስጣዊ ችግሮች በመቋቋም አንድነቱን ሊያጠናክር ይገባል። ለውጫዊ ጠላቶች በር የሚከፍቱ የተዛቡ አመለካከቶቹን በሰከነ መንፈስ ተነጋግሮ መፍታት ይጠበቅበታል። ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ሁነቶችና አስተሳሰቦችን በመከወን ትንንሾቹን ልዩነቶች ወደጎን በመተው ትልቁን አንድነት ሊያጠናክር ይገባል።

Published in ርዕሰ አንቀፅ

ኢትዮጵያ ፋሺስት ጣሊያንን ድል የነሳችበት የአደዋ የድል በዓል ለመቶ ሃያ ሁለተኛ ጊዜ ስታከበር በስፖርቱ ዓለም በጉጉት በሚጠበቀው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮናም ብርቅዬ አትሌቶቿ ትልቅ ድል አስመዝግበዋል። በእንግሊዝ በርሚንግሃም ከትናንት በስቲያ ምሽት 5ሰዓት ከ15 ላይ ቻምፒዮናው ሲጀመር በተካሄደው የሴቶች ሦስት ሺ ሜትር ውድድር አትሌት ገንዘቤ ዲባባ 8:45.05 በሆነ ሰዓት የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አስመ ዝግባለች።
ያለፈውን የውድድር ዓመት መጥፎ ጊዜ ያሳለፈችው ገንዘቤ ዘንድሮ በጥሩ አቋም ወደ ውድድር ተመልሳ በቻምፒዮናው ታሪክ አራተኛ የወርቅ ሜዳሊያዋን ማጥለቅ ችላለች። የአምስት ሺ ሜትር የዓለም ቻምፒዮኗ ኬንያዊት አትሌት ሔለን ኦቢሪና ያለፈው ተመሳሳይ ቻምፒዮና የአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር አሸናፊዋ ትውልድ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድ አትሌት ሲፈን ሃሰንን ጨምሮ አስራ ሦስት የዓለማችን ጠንካራ አትሌቶች በተሳተፉበት ውድድር ገንዘቤ ዲባባ በአስደናቂ ብቃት ተፎካካሪዎቿን አንበርክካለች።« ይህ ቀን የእኔና የአገሬ ነው፤ በዚህ ድንቅ ውድድር በማሸነፌም ተደስቻለሁ፤ ያለፈው ዓመት የእኔ አልነበረም፤ ዘንድሮ ግን የእኔ ነው» በማለት ገንዘቤ ከውድድሩ በኋላ አስተያየቷን በስፍራው ላሉ መገናኛ ብዙሃን ሰጥታለች።
ሲፈን ሃሰን ብርቱ ፉክክር አድርጋ 8:45.68 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ እንግሊዛዊቷ ላውራ ሙረንስ8:45.78 በሆነ ሰዓት ሦሰተኛ ሆና አጠናቃለች። ከገንዘቤ ጋር ኢትዮጵያን ወክላ በውድድሩ የተሳተፈችው ወጣቷ አትሌት ፋንቱ ወርቁ 8፡50.54 በሆነ ሰዓት ስድስተኛ ደረጃን ይዛ ብታጠናቅቅም ያሳየችው ብቃት አበረታች ነበር።
የታላላቅ እህቶቿን ወርቃማ ኦሊም ፒያኖች እጅጋየሁና ጥሩነሽ ዲባባ ፈለግ ተከትላ በመካከለኛ ርቀት የስኬት ማማ ላይ የደረሰችው ገንዘቤ ዲባባ እኤአ 2012 ቱርክ ኢስታንቡል ላይ በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር 4፡05፡78 በሆነ ሰዓት የመጀመሪያ የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቋ ይታወ ሳል። ከዚያም በኋላ 2014 ፖላንድ ሶፖት ላይ በሦስት ሺ ሜትር 8፡55፡54 ሰዓት ሁለተኛ የወርቅ ሜዳሊያዋን ማጥለቅ ችላለች። ባለፈው የ2016 ፖርት ላንድ ዩጂን ቻምፒዮናም በሦስት ሺ ሜትር 8፡47፡43 ሰዓት ሦስተኛ የወርቅ ሜዳሊያዋን ከቻም ፒዮናው አግኝታለች። የዘንድሮው ድሏ ሲታከልበትም በቻም ፒዮናው ታሪክ አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ሦስተኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ሆና ከጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴና ከመሰረት ደፋር እኩል የሚያደርጋትን ታሪክ አኑራለች። ገንዘቤ በዚሁ ቻምፒዮና እሁድ በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ስትወዳደር ድል ከቀናትም ይህን ክብረወሰን የምታሻ ሽልበት አጋጣሚ ይኖራል። በዚህ ቻምፒዮና ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ ከወንድ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚስተካከለው የለም። በሴቶች ደግሞ መሰረት ደፋር አራት የወርቅ፤ ሁለት የብርና አንድ የነሐስ ሜዳሊያ በማጥለቅ ከየትኛውም ኢትዮጵያዊ አትሌት በላይ ትልቅ ታሪክ አላት።

 አስመራጭ ኮሚቴው ስልጣኑን በፊፋ ሊነጠቅ ይችላል

ካለፈው ጥቅምት ሰላሳ ቀን ጀምሮ ይካሄዳል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንታዊና ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫ በበርካታ ውዝግቦች ታጅቦ ለሦስተኛ ጊዜ መራዘሙ ይታወሳል። ይሁን እንጂ በውዝግቡ ፊፋና ካፍን የመሳሰሉት ዓለምአቀፋዊና አህጉራዊ የእግር ኳስ ተቋማት ጣልቃ መግባታቸውን ተከትሎ ዛሬ በእርግጠኝነት በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ይካሄዳል የሚል እምነት በብዙዎች ዘንድ አድሮ ነበር። ሆኖም የዓለምን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራው ፊፋ ሰሞኑን ለፌዴሬሽኑ በላከው ደብዳቤ ጠቅላላ ጉባዔውና ምርጫው እንዳይካሄድ ወስኗል።
የፊፋ ዋና ፀሐፊዋ ፋቲማ ሳሙራ በላከችው ደብዳቤ መሰረት ምርጫው የሚካሄድበት ቀን ባይቆረጥም መጋቢት አጋማሽ ላይ እንደሚካሄድ ይጠበቃል። ፊፋ ምርጫው እንዲራዘም የወሰነው በአስመራጭ ኮሚቴው በኩል የሚነሳው ውዝግብና ሁለት ፅንፍ ይዞ የተከፈለው አካሄድ ተገቢ ባለመሆኑ ምክንያት ነው። ይህ አካሄድ ያልተዋጠለት ፊፋ ውዝግቦችን ለማጥራት ከሳምንት በኋላ የራሱን ባለሙያዎች ወደ አዲስ አበባ ልኮ ካጣራና የምርጫውን አካሄድ ካስቀመጠ በኋላ ምርጫው መካሄድ እንዳለበትም አሳውቋል። አስመራጭ ኮሚቴው ጠቅላላ ጉባዔው ከመካሄዱ አሥራ አምስት ቀናት ቀደም ብሎ ለጠቅላላ ጉባዔው አባላት አጀንዳዎችን በመላክ ማሳወቅ የሚጠበቅበት ቢሆንም ዛሬ ምርጫው ይካሄዳል ተብሎ ከታሰበበት ሦስት ቀናት ቀደም ብሎ እንኳን የጥሪ ደብዳቤ አልተበተነም ። የፊፋም ደብዳቤ ይህ ተገቢ እንዳልሆነ በመጥቀስ እንዲህ ዓይነት መሰል ችግሮች ሳይስተካከሉ ምርጫው መከናወን እንደሌለበት አሳስቧል። ካፍ ግን ዛሬ ሊካሄድ በነበረው ጉባዔ ላይ ተወካይ እንደሚልክ ማረጋገጫ ሰጥቶ እንደነበር ታወቋል።
ፊፋ ይህን እርምጃ ይውሰድ እንጂ እንደተ ለመደው አስመራጭ ኮሚቴው በሁለት ተከፍሎ አንዱ ፊፋ ምንም አያገባውም ምርጫው ይካሄድ፤ ሌላኛው ፅንፍ ደግሞ የፊፋ ህግ መጠበቅ አለበት የሚል ንትርክ መፈጠሩ አልቀረም። የምርጫ ቀኑን አስመራጭ ኮሚቴው ሳይሆን ሥራ አስፈጻሚና ፊፋ እየተነጋገሩ መወሰናቸው አነጋጋሪ ሆኗል። ፌዴሬሽኑ ምርጫውን ለማካሄድ ከፊፋ ይሁንታ ለማግኘት ከቀናት በፊት በ አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ ፊርማ ደብዳቤ እንደፃፈ መረጃዎች ወጥተዋል። አቶ ሰለሞን የኮሚቴው ፀሐፊ ስለሆኑ ነው ቢባልም እየተነጋገሩ የነበሩት ከኮሚቴው ሰብሳቢ ጋር ሳይሆን ከፕሬዚዳንቱ ጋር መሆኑ አስመራጭ ኮሚቴው እንደ ጉባዔተኛው እየተነገረው መገኘቱ ግርታን ፈጥሯል። በኮሚቴው ውሳኔ የካቲት 15 እና 16 የጥሪ ደብዳቤው ለጉባዔተኛው አለመላኩ የአስመራጭ ኮሚቴው ውሳኔ አቅም አልባ መሆኑን ያሳያል የሚሉ ወገኖችም አሉ።
ከዚህ በኋላ ፊፋ ምርጫው ላይ በቀጥታ ጣልቃ እንደሚገባ የላከው ደብዳቤ ይዘት ያረጋግጣል። ይህም ቀጣዩ የምርጫ ሂደትና ዕጣ ፋንታው በጉጉት እንዲጠበቅ ከማድረጉ በተጨማሪ በርካታ የስፖርት ቤተሰቦችን ያሳሰበ አጀንዳም ሆኗል። ፊፋ አጣሪ ኮሚቴውን ሲልክ በሁለት የተከፈለው አስመራጭ ኮሚቴም ይሁን እያነታረከ ምርጫውን ሲያጓትት የነበረው የዕጩዎች ተገቢነት ጉዳይ እልባት እንደሚያገኝ ይጠበቃል። ይህ እንደ መልካም ዜና የሚነሳ ቢሆንም አስመራጭ ኮሚቴው ገለልተኛ ሆኖ በአንድ አቋም ምርጫውን መምራት ሲገባው ያሳየው ዝርክርክነት አገርን በፊፋ ትዝብት ውስጥ የጣለ ስለመሆኑ በርካቶችን አሳዝኗል። ከዚህ በኋላም ምርጫውን አስመራጭ ኮሚቴው ሳይሆን የፊፋ ሰዎች እንደሚመሩት ይጠበቃል። ይህም ማለት አስመራጭ ኮሚቴው በምርጫው ላይ ያለውን አቅምና ስልጣን ባለመጠቀሙ ለፊፋ ሰዎች አሳልፎ እንዲሰጥ ሊያስገድደው ይችላል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የካፍ መስራች አባል ከመሆኗ ባሻገር ፌዴሬሽኑም በአፍሪካ አንጋፋው ወይንም የመጀመሪያው እግር ኳስ ፌዴሬሽን ነው ማለት ይቻላል። ከዚህም በተጨማሪ ከአገር አልፎ ካፍን በፕሬዚዳንትነት መምራት የቻሉና ፊፋ ውስጥ ትልቅ ተሰሚነት የነበራቸው ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ አገር ሆና በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ መገኘቷ አሳዛኝ ነው። ሌላው ይቅርና ምርጫው ከፊፋ እውቅና ውጪ ይደረግ ወይንም ፊፋ ምንም አያገባውም የሚል ሥራ አስፈፃሚ ወይንም ዕጩ እግር ኳሱን ለመምራት መዘጋጀቱ በራሱ የተዳፈነውን የአገራችንን እግር ኳስ በቀጣይ ወዴት ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው የስፖርት ቤተሰቡ ስጋት ሆኗል።

ቦጋለ አበበ

Published in ስፖርት

የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና እኤአ 1985 ፈረንሳይ ፓሪስ ተጀመረ። በአትሌቲክስ ዓለም ሁለተኛው ትልቅ ውድድር የሆነው የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ፈረንሳይ ላይ ሲጀመር የዓለም የቤት ውስጥ ጨዋታዎች የሚል ስያሜ ይዞ የነበረ ቢሆንም 1987 ላይ አሁን ያለውን የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና በሚል ስያሜ እስካሁን በየሁለት ዓመቱ እየተካሄደ ይገኛል። እኤአ 2003ና 2004 ላይ ግን በተከታታይ ዓመታት ተካሂዷል።ይህም የሆነበት ምክንያት ዋናው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ከሚካሄድበት ሙሉ ቁጥር ዓመት ጋር እንዳይጋጭ ለማድረግ ነው። ኢትዮጵያ በዚህ መድረክ ከመጀመሪያው አንስቶ መካፈል ባትችልም በውድድሩ ታሪክ በርካታ ሜዳሊያ በመሰብሰብና ውጤታማ በመሆን በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ አገራት መካከል አንዷ መሆን ችላለች። አሜሪካ ባለፉት አስራ ስድስት ቻምፒዮናዎች ከመድረኩ መቶ አስራ አራት የወርቅ፤ ስልሳ ዘጠኝ የብርና ሰባ አንድ የነሐስ ሜዳሊያ በመሰብሰብ በሁለት መቶ ሃምሳ አራት ሜዳሊያዎች ቀዳሚውን ቦታ ይዛለች። ሩሲያ ሃምሳ ሁለት የወርቅ፤ አርባ ስምንት የብርና አርባ አምስት የነሐስ በድምሩ መቶ አርባ አምስት ሜዳሊያዎች በመሰብሰብ ትከተላለች። ኢትዮጵያ በሃያ ሦስት የወርቅ፤ ዘጠኝ የብርና አስራ ሦስት የነሐስ በአጠቃላይ አርባ አምስት ሜዳሊያዎች በማግኘት ሦስተኛ ደረጃ ላይ ትቀመጣለች። ኢትዮጵያ በዚህ መድረክ ተሳታፊ መሆን የቻለችው እኤአ ከ1989 ሃንጋሪ ቡዳፔስት ከተካሄደው ቻምፒዮና አንስቶ ቢሆንም ሜዳሊያ ውስጥ መግባት የቻለችው ዘግይታ ነው። የቅርብ ተፎካካሪዋ ኬንያ በመድረኩ ከመጀመሪያ አንስቶ መካፈል እንደመቻሏ መጠን አስር የወርቅ፤ አስራ አራት የብርና አስራ አራት የነሐስ ሜዳሊያዎችን ይዛ አስራ ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧ አስገራሚ ነው።ኢትዮጵያ በውድድሩ ሜዳሊያ ማስመዝገብ የቻለችው እኤአ ከ1997 የፓሪስ ቻምፒዮና አንስቶ እንደመሆኑ መጠን አሁን ያለችበት ደረጃ ወይንም የሰበሰበችው ሜዳሊያ ብዛት በመድረኩ ውጤታማ እንደሆነች ማሳያ ነው።
የመጀመሪያው ሜዳሊያ የተመዘገበው በጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ሲሆን በሦስት ሺ ሜትር 7፡34፡71 እስካሁን ድረስ የቻምፒዮናው ክብረወሰን የሆነው ሰዓት በማስመዝገብ ነበር የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቅ የቻለው። ይህም ብቸኛ የወርቅ ሜዳሊያ ኢትዮጵያ በውድድሩ ከዓለም አስረኛ ደረጃን ይዛ እንድታጠናቅቅ አስችሏታል። ከሁለት ዓመት በኋላ ኃይሌ 1999 ጃፓን ሜባሺ ላይ በተካሄደው ቻምፒዮና ሜዳሊያ ውስጥ የገባ ሌላ ኢትዮጵያዊ አትሌት ከማስከተሉ በተጨማሪ ታሪክ የሰራበት ወቅት ነበር። ኃይሌ በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር 3፡33፡77 እስካሁንም የቻምፒዮናው ክብረወሰን የሆነ ሰዓት በማስመዝገብ የወርቅ ሜዳሊያ ሲያጠልቅ ሚሊዮን ወልዴ 7፡53፡79 በሆነ ሰዓት የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆኗል። በሦስት ሺ ሜትርም ኃይሌ 7፡53፡57 ሰዓት አስመዝግቦ በውድድሩ ታሪክ በአንድ ጊዜ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ማጥለቅ ችሏል። ይህም ኢትዮጵያ በውድድሩ በሁለት ወርቅና አንድ ነሐስ ከዓለም ስድስተኛ ደረጃን እንድትይዝ አስችሏታል። ቀጣዩ ታሪክ ዘንድሮ ቻምፒዮናውን የምታስተናግደው የእንግሊዟ ከተማ በርሚንግሃም ላይ የተከናወነ ነው። እኤአ 2003 ኃይሌ በዚህች ከተማ በሦስት ሺ ሜትር 7፡40፡97 በሆነ ሰዓት አራተኛ የወርቅ ሜዳሊያውን ሲያጠልቅ በተመሳሳይ ርቀት ብርሃኔ አደሬ 8፡40፡25 በሆነ ሰዓት የወርቅ ሜዳሊያ አጥልቃ በቻምፒዮናው ታሪክ በሴቶች የመጀመሪያዋ የሜዳሊያ ባለቤት ሆናለች። መሰረት ደፋር ደግሞ 8፡42፡58 በሆነ ሰዓት የነሐስ አሸናፊ ነበረች። ይህም ኢትዮጵያን ከዓለም አምስተኛ ደረጃ ላይ ሊያስቀምጣት ችሏል። ከዚህ በላይ ግን በውድድሩ ፈር ቀዳጅ የነበረው ኃይሌ የወርቅ ሜዳሊያ ስብስቡን አራት በማድረስ ትልቅ ታሪክ የሰራበት ሆኖ ይታወሳል። በዓመት ልዩነት ሃንጋሪ ቡዳፔስት ዳግም ያዘጋጀችው ቻምፒዮናም ለኢትዮጵያ ውያን አዲስ ታሪክ የተመዘገበበት ነው። ቁጥሬ ዱለቻ በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር በሴቶች በታሪክ የርቀቱ የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ድል ሆኖ ሲመዘገብ ርቀቱን አጠናቅቃ የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀችበት ሰዓት 4፡06፡40 ነበር። በተመሳሳይ ርቀት አትሌት ማርቆስ ገነቲ በወንዶች የነሐስ ሜዳሊያ ያጠለቀበት ሰዓት 7፡57፡87 ሆኖ ተመዝግቧል። የሴቶች ሦስት ሺ ሜትር ውድድርም በኢትዮጵያውያኑ ብርሃኔ አደሬና መሰረት ደፋር ፉክክር የደመቀ ነበር። ከዓመት በፊት ነሐስ አጥልቃ የነበረችው መሰረት 9፡11፡22 በሆነ ሰዓት ወደ ወርቅ ስትሸጋገር ብርሃኔ በአስራ አንድ ማይክሮ ሰከንድ ዘግይታ የብር ሜዳሊያ ወስዳለች። ኢትዮጵያም ከዓለም ሦስተኛ ደረጃን ይዛ ተመልሳለች።
2006 በሩሲያ ሞስኮ ቻምፒዮናም በሦስት ሺ ሜትር ቀነኒሳ 7፡39፡32 ሰዓት፤ መሰረት ደፋር 8፡38፡80 ሰዓት ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎች ቢመዘገቡም ኢትዮጵያ ከዓለም የነበራትን የሦስተኛነት ደረጃ አላስነጠቀችም። በቀጣዩ የ2008 ስፔን ቫሌንሲያ ቻምፒዮና ኢትዮጵያ ከዓለም ሦስተኛ ደረጃን ይዛ ብትጨርስም በርካታ ሜዳሊያዎች ተመዝግበዋል። ደረሰ መኮንን በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር 3፡38፡23 ሰዓት የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሲሆን ታሪኩ በቀለ በሦስት ሺ ሜትር 7፡48፡23 ሰዓት ሌላ የወርቅ ሜዳሊያ አስመዝግቧል። በዚሁ ርቀት አብርሃም ጨርቆስ 7፡49፡96 ሰዓት የነሐስ ሜዳሊያ ማስመዝገብ ችሏል። በሴቶች አንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ገለቴ ቡርቃ እስካሁን የቻምፒዮናው ክብረወሰን የሆነውን 3፡59፡75 ሰዓት በማስመዝገብ የወርቅ ሜዳሊያ ስታጠልቅ መሰለች መልካሙ 8፡41፡50 በሆነ ሰዓት የብር ሜዳሊያ አሸናፊ መሆን ችላለች።
2010 ኳታር ዶሃ በተካሄደው ቻምፒዮና ደረሰ መኮንን የአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ድሉን ለሁለተኛ ጊዜ ሲያጣጥም በተመሳሳይ ርቀት ቃልኪዳን ገዛኸኝ 4፡08፡14 በሆነ ሰዓት የወርቅ ሜዳሊያ አጥልቃለች። ገለቴ ቡርቃም 4፡08፡39 በሆነ ሰዓት የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ ነበረች። መሰረት ደፋር ከአራት ዓመት በኋላ ወደ መድረኩ ተመልሳ በሦስት ሺ ሜትር 8፡51፡17 ሰዓት አራተኛ የወርቅ ሜዳሊያዋን ባጠለቀችበት ውድድር ስንታየሁ እጅጉ 8፡52፡08 በሆነ ሰዓት የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆናለች። በነዚህ ድሎችም ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። ቀጣዩ 2012 የቱርክ ኢስታንቡል ቻምፒዮና ኢትዮጵያ ከመካከለኛ ርቀቶች በተጨማሪ ውጤቷ በአጭር ርቀትም የታጀበ ነበር። መሐመድ አማን በስምንት መቶ ሜትር 1፡48፡36 ሰዓት በማስመዝገብ በዓለም አቀፍ ደረጃ በርቀቱ የመጀመሪያ ድል ለኢትዮጵያ አስመዝግቧል። በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ሴቶች ገንዘቤ ዲባባ 4፡05፡78 በማስመዝገብ የወርቅ ሜዳሊያ ስታጠልቅ፤ መሰረት ደፋር በሦስት ሺ ሜትር 8፡38፡26 አስመዝግባ የብር ሜዳሊያ ወስዳለች፤ በዚሁ ርቀት ገለቴ ቡርቃ 8፡40፡18 በሆነ ሰዓት የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ ነች። በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ወንዶችም ደረሰ መኮንን 3፡45፡90 በመግባት የነሐስ ሜዳሊያ አጥልቋል። ኢትዮጵያም በነዚህ ሜዳሊያዎች ሦስተኛ ደረጃን ከዓለም በመያዝ ጨርሳለች። የ2014 ፖላንድ ሶፖት ቻምፒዮና ላይ ከሁለት ዓመት በፊት የታየው የኢትዮጵያ አዲሱ ትውልድ የወርቅ ሜዳሊያ ምንጭ ሆኗል። መሀመድ አማን ስምንት መቶ ሜትሩን 1፡46፡40 በማገባደድ ዳግም በርቀቱ ሲነግስ ገንዘቤ ዲባባም በተመሳሳይ በሦስት ሺ ሜትር 8፡55፡54 አስመዝግባ ባለ ድል ሆናለች። በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር አማን ወጤ 3፡38፡08 በሆነ ሰዓት የብር ሜዳሊያ፤ በሦስት ሺ ሜትር ደጀን ገብረመስቀል 7፡55፡39 ሰዓት የነሐስ፤ በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር አክሱማዊት አምባዬ 4፡07፡12 ሰዓት የብር ሜዳሊያ አስመዝግበው ኢትዮጵያ ከዓለም ሦስተኛነቷን ማስጠበቅ ችላለች። ያለፈው የ2016 ፖርትላንድ ዩጂን ቻምፒዮና ዮሚፍ ቀጄልቻ በሦስት ሺ ሜትር 7፡57፡21 በሆነ ሰዓት የወርቅ ሜዳሊያ ሲያስመዘግብ በተመሳሳይ ርቀት ገንዘቤ ዲባባ 8፡47፡43 ሰዓት የወርቅ፤ መሰረት ደፋር ደግሞ 8፡54፡25 ሰዓት የብር ሜዳሊያ ማጥለቅ ችላለች። በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ሴቶች ወጣቶቹ አትሌቶች ዳዊት ስዩም 4፡05፡30 ሰዓት የብር፤ ጎደፋይ ፀጋዬ 4፡05፡71 የነሐስ ሜዳሊያ አጥልቀው ኢትዮጵያ ከሁለት ቻምፒዮናዎች በኋላ ከዓለም ሁለተኛ ደረጃዋን መልሳ አግኝታለች።
በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ሞዛምቢካዊቷ የስምንት መቶ ሜትር አትሌት ማሪያ ሞቶላ እኤአ ከ1993 እስከ 2008 ሰባት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ቀዳሚ ስትሆን፤ ሩሲያዊቷ የአራት መቶ ሜትርና አራት በአራት መቶ ሜትር ዱላ ቅብብል ከ1999 እስከ 2008 የነገሰችው ናታልያ ናዛሮቫ ተመሳሳይ ታሪክ ትጋራለች። ከ1993 እስከ 2001 በርዝመት ዝላይ ስኬት ላይ የነበረው ኩባዊው ኢቫን ፔድሮሶ በአምስት ተከታታይ ቻምፒዮናዎች ወርቅ በማጥለቅ ይታወቃል። ቡልጋሪያዊቷ ከፍታ ዘላይ ስቲፍካ ኮስታዲኖቫ አምስት የወርቅ ሜዳሊያዎች ያጠለቀች ሌላኛዋ አትሌት ናት። ከዚህ ቀጥሎ ግን ኃይሌ ገብረስላሴ አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ የሚጠቀስ አትሌት ነው። እውቁ የሶቬት ህብረት ከዚያም የዩክሬን ምርኩዝ ዘላይ ሰርጌ ቡካ፤ ኩባዊው ከፍታ ዘላይ ጃቪየር ሶቶማዮር አራት ወርቅና አንድ ነሐስ በማጥለቅ፤ ስዊድናዊው ከፍታ ዘላይ ስቲፋን ሆልም አራት የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ ተመሳሳይ ታሪክ ይጋራሉ። መሰረት ደፋርም አራት የወርቅ፤ ሁለት የብርና አንድ የነሐስ ሜዳሊያ በማጥለቅ ከነዚህ አትሌቶች የተሻለ ታሪክ ያላት ስትሆን የሚስተካከላት ሌላ ኢትዮጵያዊ አትሌት የለም።

ቦጋለ አበበ

Published in ስፖርት
Saturday, 03 March 2018 21:44

የትናንት ስንቅ

    “ይህንን ውል ብዬ ከምቀበል ሞትን እመርጣለሁ” በማለት ፈፅሞ በኢትዮጵያ ነፃነት እንደማይደራደሩ የማይናወፅ አቋማቸውን ለጣሊያኖች አሳይተዋል፤  የእኛዋ  የሴት ጀግና እቴጌ ጣይቱ። እቴጌ ጣይቱ ይህንን ቆራጥ ንግግር ከአንደበታቸው ያወጡት ጣሊያኖች  የተሳሳተውን የው ጫሌውን ውል ይዘው አላስተካክል ባሉ ጊዜ እንደነበር የታሪክ ሙሁራን ይናገራሉ፤ መዛግብትም ይህንኑ ያብራራሉ።
ኢትዮጵያውያን  ዘመናዊ ወታደራዊ ስልጠና የወሰደውንና ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታጠቀውን ወራሪ የጣሊያን ጦር  አድዋ ላይ አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ካስመዘገቡት ድል በስተጀርባ የእቴጌ ጣይቱ ሚና ትልቅ ነበር። እቴጌ ጣይቱ ሴቶችን በማስተባበር በስንቅ አቅርቦቱ፣ የተጐዱትን በማንሳትና በማከሙ፣ ድንቅ የጦርነት ሀሳቦችን በማፍለቅ  ለአድዋ ድል መገኘት የማይተካ ሚና መጫወታቸውንም የታሪክ ድርሳናት ይነግሩናል።:
እቴጌ ጣይቱ  ጀግንነትን አስተምረ ውናል፤ የዓላማ ጽናትን ትተውልናል። አይበገሬነትን አሳይተውናል። ታሪክ ሰርተው ታሪክ ትተው አልፈዋል። እኛ ሴቶችም በነበረው ብቻ ሳይሆን ዛሬም በርካታ ታሪኮች መስሪያ ወቅት ላይ ነን። የጦርነት ታሪክ ብቻ ሳይሆን የልማት አርበኛነት ይጠብቀናል። ከእነ እቴጌ ጣይቱ  ምን ተም ረናል?
እናት አርበኛ እህተ ታከለ በተወለዱ በአንድ ወራቸው በእናታቸው ጀርባ ታዝለው መዝመ ታቸውን ይናገራሉ። የዛሬ 81 ዓመት መወለ ዳቸውን ቀን ቆጥረው  መዝገብ አገላብጠው ሳይሆን  ወላጆቻቸው የነገሯቸውን ጣሊያን አገሪቷን የወረረችበትን ጊዜ በማስታወስ ብቻ ልደታቸውን ይቆጥራሉ።  እርሳቸው ራሳቸውን ማወቅ ከጀመሩ በኋላ  ጣሊያን ድል ተመትቶ ከአገራችን የወጣበትን የድል ቀን  በመያዝ የድል በዓል ላይ አምስት አመት የጣሊያን ቆይታ በመጨመር ብቻ በምድር ላይ የኖሩበትን  ዕድሜያቸውን ያሰላሉ። «አሁን ይሄው 81 ዓመት ሞላኝ። ያኔ ህፃን ሆኜ በእቅፍ  ከእናቴ ጋር  ዘምቻለሁ። ወላጆቼ  ታሪክ ሰርተው የአገራችንን ዳር ድንበር ጠብቀው  ለእኛ አስተላልፈዋል። እኔም የእነሱን አደራ ተረክቤ ታሪክ በማስቀጠል ላይ ነኝ፡፡» በማለት ለአገራቸው ያላቸውን ፍቅርና ክብር ይገልፃሉ።
አርበኞች  በጫካ፣ በዱር ተንከራተው መሳሪያ ሳይኖራቸው  ጣሊያንን ያሸነፉት አንድነት ስለነበራቸው፤ አገራቸውን ይወዱ፣ መሪያቸውን ያከብሩ ስለነበር ነው። በአንድነት፣ በፍቅር ተራመደው አገሪቷን ከጠላት ጠብቀዋል፤ አሁን ደግሞ  የአገሪቷን  ሰንደቅ ዓላማ ለወጣቱ  ተተኪ ትውልድ አስተላልፈዋል። አሁን በአገሪቷ ላይ ከውጪ የመጣ ጠላት የለም፤ ኢትዮጵያ አንድ ናት። ስለዚህ  አንዲት አገርን በአንድነት ጠብቆ ዳር ድንበሯን አስከብሮ ታሪክን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል ይላሉ። ለዛሬ ትውልድም መልዕክታቸው «የአባት አያቶቻችንን ታሪክ ይዘን  ይሄው  አገራችንን እየጠበቅን ነው። እናንተም የእኛን አደራ ተረከቡ» ይላሉ።
እናት አርበኛ እህተ  እንዳሉት ሴቶች  በጦር ሜዳ ብቻም ሳይሆን በሌሎችም   ስራዎች ላይ  ተሰማርተው  ጥሩ  እየሰሩ መሆናቸውን ይጠቅ ሳሉ። ሴቶች   ሀኪም ናቸው፤ መምህር ናቸው፤ በምድርም  ሆነ በአየር የሚበረውን  ሁሉ እየሰሩ ናቸው። የቀደምት እናት አርበኞችን  ሞራል ይዘውም እየሰሩ ናቸው ይላሉ።
«አድዋ  የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ሄጃለሁ። ያኔ አያት አባቶቻችን ከጣሊያን ጋር ተዋግተው ደማቸውን ያፈሰሱበትን አጥንታቸውን የከሰከሱበትን ቦታ ለማየት ችያለሁ። ዘንድሮ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ በእዛው ተገኝቻለሁ» በማለትይናገራሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶችና ህፃናት  ቢሮ ሀላፊ  ወይዘሮ አለምፀሀይ ኤልያስ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የአድዋ ድል የሴቶች የድል ውጤት ጭምር ነው። በሁሉም መስክ ከሁሉም ስኬት በስተጀርባ  ሴቶች አሉ። ሴቶች በጦር ሜዳ ከመዋጋት አንስቶ  ስንቅ በመሰነቅ፣ በጀርባ ሆነው በቀረርቶ፣ በፉከራ፣ ወኔ በማነሳሳትና ጦሩ  ወደ ፊት  እንዲሄድ ሀይል በመሆን  በጦርነት አውዱ የሴቶች ሚና ትልቅ እንደነበር ይጠቅሳሉ።
እቴጌ ጣይቱ ስመጥር አርበኛ ናቸው፤ የጦር አበጋዝ  ለጦሩ ስንቅ እያቀበሉ፣ የተመታውን ቁስል እያሰሩና እያስታመሙ ከወንዱ እኩል ታሪክ የሰሩ ጀግና ናቸው። ከዛ የምንማረው አንድ ነገር አለ ይላሉ ወይዘሮ አለምጸሀይ ያኔ ውጊያው ከጠላት ጋር ነው። አሁን ግን ውጊያ የሚደረገው ከድህነት፣ ከአመለካከት፣  ከአስተሳሰብ ጋር  ነው። በጋራ በምንገነባው የአንድ ፖለቲካ ማህበረሰብ   የሴቶች ሚና ከፍ ሊል ይገባል። ያኔም ሴቶች  ሆ ብለው  ወጥተው  ለውጤት በቅተዋል። ዛሬም በቋንቋ፣ በብሄር  ባለመከፋፈል አንድ  በመሆን  የአገሪቷንና የህዝቦቿን  አንድነት መጠበቅ ያስፈልጋል። አንድ ሰው የትም ሊወለድ ይችላል። እዛ ቦታ የሚወለደው ፈልጎ አይደለም። ስለዚህ ማንም ከየትኛውም አቅጣጫ ይምጣ  የአንድ አገር ልጅ ነው፡፡ አንድ ሀሳብና አስተሳሰብ እንዲኖር በማድረግ እናት የልጆቿን አስተሳሰብ ቀርፃ ማሳደግ እንዳለባት ይመክራሉ።
በአድዋ ጦርነት ወቅት ከጦርነቱ በስተጀርባ ሴቶች ነበሩ፡፡ ከልጆቻቸው ጀርባ እናቶች  ነበሩ። ያንን ወቅት በድል መወጣት ተችሏል። አሁንም ብቅ  ብቅ እያሉ  ልዩነትን የሚዘሩ ነገሮች ላይ  እናቶች የልጆቻቸውን አስተሳሰብ   በመቅረፅ ሊያስተካክሉት ይገባል። አለም አንድ መንደር በሆነችበት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያዊነት  ምን ማለት እንደሆነ ማሰብ ያስፈልጋል። ከዛ ውጪ በመንደርና ጎጥ  መለያየትን ወቅቱ አይፈቅድም። ስለዚህ  እናቶች ይህንን አስተሳሰብ በመቅረጽ በድል መወጣት ይጠብቃቸዋል ይላሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ታሪክ እና በኢትዮጵያ የሥነ - ጥበባት ታሪክ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው (ባለፈው ዓመት ካዘጋጁት )፤ እቴጌ ጣይቱ በአድዋ ዘመቻ ወቅት የራሳቸውን ጦር እየመሩ በመዝመት ለድሉ የማይተካ ሚናን መጫወታቸውን ያስታውሳሉ። ከእነዚህ ተግባራት መካከል የመጀመሪያው የስንቅ አቅርቦቱን በአግባቡ እንዲከናወን በማድረግ ሠራዊቱ በረሃብ ምክንያት እንዳይበተን ማድረግ መቻላቸው አንዱ መሆኑንም ይገልፃሉ:፡
እቴጌ ጣይቱ የዘር ሐረጋቸው፣ ከየጁ፣ ከስሜን፣ ከደብረ ታቦር፣ ከጐጃም አዴት ሁሉ የሚመዘዙ በመሆናቸው ለሠራዊቱ ከእነዚህ አካባቢዎች የምግብ እህል ብቻ ሳይሆን ለጋማ ከብቶች ጭምር ሣር እየተጫነ እንዲመጣ በማድረግ ሠራዊቱን ከሴቶች ጋር በመሆን እያበሰሉ ይቀልቡ ነበር:: ይህ ሚናቸው ጣሊያኖች እንዳሰቡት የኢትዮጵያ ጦር በቀላሉ ሳይበተን አድዋ ላይ ተዋግቶ ድል እንዲያገኝ አስችሏል።
በጦርነቱ ድል የተገኘ ቢሆንም ከባድ እና አሰቃቂ የአካል ጉዳትና ሞት ያሥከተለ በመሆኑ ቁስለኞችን የማከሙን፣ እህልና ውኃ የመሥጠቱን እንዲሁም እስከሬኖችን የመሰብ ሰብና የመለየቱን ተግባራት ሴቶችን እና ሰራዊታቸውን በማሥተ ባበር በትጋት እንደ ተወጡም ይጠቅሳሉ።
ጦርነቱ በተለያዩ አቅጣጫዎች ይደረግ ስለነበር በአንዱ አቅጣጫ የዘመተው አዝማች ድል አድርጐ እና ምርኮ ይዞ በመመለስ ሲፎክርና ሲያቅራራ ድሉ ገና ሙሉ በሙሉ ያልተረጋገጠ በመሆኑ፤ “ንጉሰ ነገሥቱ ሣይመለሱ እዚህ ሆኖ መፎከሩ ምንድነው?” በማለት እየተቆጡ እና እያበረታቱ ሌሎችን ሄደው እንዲረዱ ማድረጋቸው ሌላው ሚናቸው መሆኑንም ተገልጿል::
ከዚህም ባሻገር ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሽንፈትን የተጐነጩት ጣሊያኖች ወደ መቀሌው ምሽግ በመክተት እና የመቀሌውን ምሽግ እንዳይደፈር አድርገው በግንብ፣ በእሾሃማ ሽቦ፣ በሹል እንጨቶች፣ በብርጭቆ ስብርባሪዎች በማጠር በባዶ እግሩ የሚዋጋው የኢትዮጵያ ሠራዊት እንዳይጠጋቸው ለማድረግ ሞክረዋል። ሆኖም ይህን ሁኔታ የተገነዘቡት እቴጌይቱ የጣሊያኖችን የውኃ ምንጭ በራሳቸዉ ጦር በማስከበብ ከውኃ ጋር እንዲቆራረጡ በማድረግ ሳይወዱ በግዳቸው በኋላ ላይ ሽንፈታቸውን እንዲጐነጩም ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ይታወሳል።
ይሄ የትናንቱ የጦርነት የድል ታሪክ ይታወሳል፤ ይዘከራል። የትናንቱ ስንቅ ለዛሬው ሆኖናልና ነገም በመቀጠል ድህነትን ድል መምታት ያስፈልጋል። የድሉንም ስንቅ ታሪክ ለነገው ማስተላለፍ የግድ ይላል።

አልማዝ አያሌው

Published in ማህበራዊ
Saturday, 03 March 2018 21:42

የአንድነት ውጤት አድዋ

ለአድዋ ጦርነት መነሻ የሆነው የውጫሌ ውል የተፈጸመው ከአዲስ አበባ ከተማ በስተሰሜን 468 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው፡፡ ወሎ ውስጥ በሚገኘው ውጫሌ ከተማ አምባሰል ተራራ ሥር ሲሆን ንጉሥ ይስማ በተባለው ሥፍራ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ማለዳ ላይ የአድዋ ድንጋያማና ወጣ ገባ በሆነው የአድዋ ኮረብታ በመሳሪያ፣ በጦር ትጥቅና ስልት የሃይል ሚዛኑ ባልተመጣጠነ ሁኔታ  የዛሬ አንድ መቶ ሃያ ሁለት ዓመታት ገደማ በአንድ አውሮፓዊና በአንድ የጥቁር ህዝብ መካከል የተካሄደው ጦርነት በሰዓታት ጊዜ በጥቁር ህዝቦች አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ አንድነት፣ ጀግንነት፣ ቆራጥነት፣ ድል የማድረግ ጽኑ ፍላጎት ለድሉ ውጤታማነት አስተዋጽኦ ማድረጉን በርካቶች ይስማሙበታል፡፡  
በወቅቱ አገሪቷን ይገዙ የነበሩት አጼ ምኒልክ በውሉ ምክንያት ግጭት ሊመጣባቸው እንደሚችል ያውቁ ነበር፡፡ ቀድመውም «የአገሬ የኢትዮጵያ ሰው ሁሉ ስማ ... እግዚአብሄር በባህር ወስኖ የሰጠንን አገር የሚያጠፋ፣ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት መጥቶብናልና ስንቅህን እያሰናዳህ ተከተለኝ፡፡ እስካሁን የበደልሁህ በደል ያለ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ለአገርህ፣ ለሚስትህ፣ ለልጅህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል ጉልበት ያለህ በጉልበትህ፣ ገንዘብ ያለህ በገንዘብህ፣ ጉልበትም ገንዘብም የሌለህ ግን በሃዘንህ እርዳኝ፡፡ ይህን አዋጅ ከሰማህ በኋላ ወስልተህ ከዘመቻው ብትቀር ትቀጣለህ፡፡ እናም በጥቅምት ወር ካዲስ አበባ እነሳለሁና፤ የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ወረይሉ ይግባ፡፡ የጎጃም፣ የበጌ ምድር፣ የደንቢያ፣ የቋራ፣ ከጨጨሆ በላይ ያለህ አሸንጌ ላይ፡፡ የሰሜን የወልቃይት፣ የጠገዴ ሰው መቀሌ ላይ ላግኝህ» ሲሉ ለሀገሩ ህዝብ መልዕክት ልከዋል፡፡
   የታሪክ ተመራማሪው ጆርጅ በርክሌይ የአድዋ ጦርነትና ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ በተሰኘው ዳኘው ኃይለሥላሴ ወደ አማርኛ በተረጐሙት መጽሐፍ፤ ሃያ ዘጠኝ ሺህ ፈረሰኞችን ጨምሮ ከመቶ ሺህ እስከ መቶ ሃያ ሺህ የሚገመት አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በባዶ እግሩ የተጓዘ የኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት በወታደራዊ አካዳሚ የሠለጠነውን የአውሮጳ ወራሪ ጦር የካቲት 23 ማለዳ አሥራ አንድ ሰዓት ገደማ ገጥሞ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ማሸነፉን አረጋግጧል ሲል ጽፏል፡፡
ጦርነቱ በተጀመረ ከአምስት ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሃምሣ ስድስቱም የኢጣሊያ መድፎች ሙሉ ለሙሉ ተማርከዋል፤ የቅኝ ገዢውን ወራሪ ሠራዊት ከመሩት ጀኔራሎች ጄኔራል አልቤርቶኒ ሲማረክ የሠራዊቱ ዋና አዛዥ ጄኔራል ባራቴሪ ከጥቂት አጃቢዎቹና በሽንፈት ከተበታተኑ የኢጣሊያ ወታደሮች ጋር ሸሽቷል፡፡
በጦርነቱ የኢጣሊያ መድፎች፣ በርካታ ቀላልና ከባድ መትረየሶች፣ የነፍስ ወከፍ ጠመንጃዎች ከበርካታ ጥይቶቻቸው ጋር ተማርከዋል፡፡ የተማረኩት የጦር መሳሪያዎችም በአምስት መቶ አጋሰሶች ተጭነው ወደ አዲስ አበባ እንዲጓጓዙ ተደርጓል፡፡ በታላቅ አሸናፊነት የተጠናቀቀው የአድዋ ድልም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር፤ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲልና የማንነት መለያ ምልክት ሆኖ አልፏል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሶስተኛ ዓመት የታሪክ ተማሪው አብዱልከሪም ተመስገን እንደሚለው፤ የአድዋ ድል አሁን ነጻነትን ያስጠበቀ፣ በባርነት ሲማቅቁ እና በቅኝ ግዛት ሲጨቆኑ ለነበሩ አፍሪካውያን መነሳሳትን የፈጠረ ድል ነው፡፡
እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ አድዋ በአገሪቱ ያመጣውን ድል ሲያስበው እንደሚያስደስተውና  እንደሚያስደንቀው የሚናገረው አብዱልከሪም፤ በየዓመቱም በዓሉን በኩራት እንደሚያከብረው ይገልጻል፡፡ እንደ አንድ አፍሪካዊ ሲያስበውም በቅኝ ግዛት ውስጥ ሲማቅቁ የነበሩ አፍሪካውያን ወንድሞቹና እህቶቹ መነሳሳት ያገኙበት እንደመሆኑ የኩራትም የደስታም ስሜት እንደሚሰማው ይጠቁማል፡፡      
 ለአድዋ ጦርነት ድል ምክንያት የሆኑ በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይናገራል፤ በወቅቱ የኢትዮጵያ ጦር የነበረው አንድነት ለድሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ብሎም ያስባል፡፡
ጣሊያኖች የተሸነፉት ብዙ ትኩረት ባለመስ ጠታቸው እንደነበር፣ ለጦሩ ብዙ ገንዘብ ፈሰስ ሳያደርጉ መሆኑንና በጥቅሉ በደንብ ሳይዘጋጁ ጦርነቱን በማካሄዳቸው እንጂ የኢትዮጵያኖች ጥንካሬ አይደለም በሚል የሚከራከሩ ሰዎች መኖራቸውን ያስታውስና፤ በከፊል ይህ እንደምክንያት ቢነሳም  ወሳኙ ምክንያት  አንድነት ነው ይላል፡፡ ጠላት ምንም የወደቀ ቢሆንም እንኳን  የሚገጥመው ሃይል አንድነት ከሌለው ማሸነፍ አይችልም፡፡ በመሆኑም የአድዋ ድል በአንድነት የተገኘ ድል ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁንም ድህነትን ልናሸንፍ የምንችልበት ዋነኛውና ብቸኛው መንገድ አንድነት መሆኑን ይጠቁማል፡፡                    
እንደ አብዱልከሪም ማብራሪያ፤ ይህ ትውልድ ከአድዋ ድል ትልቅ ትምህርት መቅሰም አለበት፡፡ አሁን ከድህነት ቀንበር ለመውጣት እየታገልን እንገኛለን፡፡ በዛን ጊዜ የነበረውን አንድነት እና የኢትዮጵያዊነት ስሜት መፍጠር ካልተቻለ የድህነት ቀንበርን ሰብረን ነጻ መውጣት አንችልም፡፡ እድገት ከተፈለገ አንድነት ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያዊነት በእያንዳንዱ ሰው  ስሜት ውስጥ ሊሰርጽ ይገባል፡፡
አለመስማማት ሲኖር ጥሩ አጋጣሚ ተፈጠረልን የሚሉ ጎረቤት አገሮች የራሳቸውን አጀንዳ በማስፈጸም የግድቡን ግንባታም ሆነ ሌሎች የተጀመሩ ልማቶችን እንዳይጠናቀቁ በማደናቀፊያነት ይጠቀሙበታል፡፡ አመጽ እንዲነሳ የገንዘብ፣ የቁሳቁስ እና የሞራል ድጋፍ ይሰጣሉ፡፡ ወጣቱ ደግሞ የእዚህ ሰለባ እየሆነ የመጣ ይመስላል፡፡ ይህንን ወጣቱ ቢያገናዝብ የተሻለ ነው ሲል ይመክራል፡፡
ፖለቲካዊ አቋምን ያለመደገፍ የማንኛውም ዜጋ መብት ነው፡፡ በምክንያት እንጂ በጭፍን ድጋፍ መስጠት ‹‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ›› አይነት አካሄድ እንደመሆኑ ለማንም ለምንም አይበጅም፡፡  ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚወስድ እርስ በርስ የሚያጫርስ አካሄድ በመሆኑ ሁሉም ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል ይላል፡፡
ሁላችንም ድህነትን ለማሸነፍ የምንሄድበት መንገድ ባለንና በተሠጠን አቅምና ችሎታ ይወሰናል፡፡ በአቅማችን ለአገሪቱ እድገት የድርሻችንን ካበረከትን ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ አብነት ሲጠቅስም እኔና ጓደኛዬ የጋራ ስሜት ካለን እኔም ጓደኛዬም እንደ ኢትዮጵያዊ የማናስብና አገራዊ ስሜትን የምንፈጥር ከሆነ ድህነትን ማሸነፍ ይቻላል ፡፡
«ድሮ የነበረው የኢትዮ ጵያዊነት ስሜት  አሁን  እየተሸ ረሸረ መጥቷል፡፡ ይህንን ማስተ ካከል ያስፈልጋል፡፡ በትምህርት ተቋማት ስለኢትዮጵያ ታሪክ አይነገርም፡፡ ይህንን ማረም ያስፈልጋል፡፡  አብዛኛው ሰው ትናንት ስራና ትምህርት ዝግ የሆነበትን ምክንያት ቢጠየቅ የሆነ በዓል ስላለ እንጂ ስለ አድዋ ድል መዘከር ምክንያቱን ባግባቡ እንደማያውቅ እገምታለሁ፡፡ ይህንን ሁኔታ በመቅረፍ ህብረተሰቡ እንዲያውቅ ለማድረግ ከህጻናት ጀምሮ መሰራት አለበት፡፡ ህጻናት ታሪካቸውን እያወቁ እንዲያድጉ መደረግ ይኖርበታል፡፡ ተግባሩ ደግሞ በአንድ አካል ላይ የሚወድቅ ሳይሆን የሁሉም ሰው ድርሻ ሊሆን ይገባል፡፡ የሀገር ስሜት መገንባት የሚጀምረው ከቤተሰብ ነውና በተለይም የእያንዳንዱ ቤተሰብ በዚህ ላይ መስራት አለበት»ይላል የታሪክ ተማሪው፡፡
በኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ብርሀኑ በላቸው፤ የአድዋ ድል ከጫፍ እስከ ጫፍ  የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተረባርበው ያገኙት ድል እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በአንጻሩ ታላቁ የህዳሴ ግድብን ከጫፍ እስከ ጫፍ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ግንባታውን እውን ለማድረግ እየተረባረቡበት እንደሚገኙ ያመለክታሉ፡፡ የአድዋ ድል የውጭ ድጋፍ ሳይኖር የተገኘ መሆኑን የሚናገሩት መምህሩ፤የህዳሴ ግድብም ያለድጋፍ በራስ አቅም እየተከናወነ እንደሚገኝ ነው፡፡ ያለ ዕርዳታ የተገኘው የአድዋ ድል የአፍሪካ ታሪክ ነው፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብም በአፍሪካ ትልቁ ግድብ እንደመሆኑ ለአፍሪካ ሌላ አድዋ  አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡ በአድዋ ድል ማግስት አንጻራዊ ሰላም ተገኝቷል፣ አጼ ምኒልክ ዘመናዊነትን እንዲያስፋፉም ዕድል ሰጥቷል፡፡ የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ ኑሮን የሚለውጥ የህዝቡን ገቢ የሚያሳድግ አንጻራዊ ሰላምንም ያመጣል፡፡አድዋ ላይ ድል የተነሳው ከውጭ የመጣ ጠላት ነው የሚሉት መምህሩ፤ በዚህ ዘመን ግድቡን በመገንባት የምናሸንፈው በውስጣችን ያለውን የድህነት ጠላት  ነው ይላሉ፡፡
መጠራጠር፣ አንዱ ሌላው ብሄር ላይ ቅሬታ የማሳየት አዝማሚያዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋሉ መሆናቸውን በማንሳት እንዲህ አይነት ሁኔታዎች አንድነትን የሚሸረሽሩ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ክስተቱ የውጭ ሃይሎች የህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎልና ለማጓተት ያደረጉት እንቅስቃሴ ውጤት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በተለይም ይህ ትውልድ በማህበራዊ ድረ ገጽ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ነቅቶ የመጠበቅ ሃላፊነት እንዳለበት ይመክራሉ፡፡
አሁን ጠያቂ ትውልድ ተፈጥሯል፡፡ ይህ በጎ ነገር በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ትውልዱ ስለጠየቀ በርካታ ለውጦች መጥተዋል፡፡ ሆኖም ጥያቄ መቅረብ ያለበት በአግባቡ ነው፡፡ የለማውን እያፈረሱ ልማትን መጠየቅ ተገቢ አይደለም፡፡ የስራ ዕድል የከፈቱ ልማቶችን እያጠፋ የስራ ዕድል መፍጠር አይቻልም፡፡ ጥያቄዎች ከስሜታዊነት በጸዳ መልኩ  መቅረብ፣ ምላሽም በአግባቡ መስተናገድ ይገባል የሚል አቋም አላቸው፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ ቅሬታዎች ከስሜታዊነት ባሻገር የውጭ ሀይሎች እጅ እንዳለበትም መታዘብ እንደ ሚቻል ያነሳሉ፡፡ የሙርሲ መንግስት በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ያስተላለፈውን  በማስ ታወስም በማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡ ተቀማጭነቱን በኤርትራ አድርጎ የትጥቅ ትግል ሲያደርግ የነበረው የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ /ቤህነን/ የኤርትራ እና የግብጽ መንግስታት ቡድኑ በህዳሴ ግድብ ላይ ጥቃት እንዲፈጽም ቢታዘዝም ትዕዛዙን ባለመቀበል ይልቁንም በአገሪቱ እየተመዘገበ ላለው ልማት አጋዥ ሀይል ለመሆን ወስኖ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ያስታውሳሉ፡፡   
ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ታሪክና ጂኦግራፊ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አስገዳጅ የትምህርት ዘርፎች ሆነው ይሰጡ እንደነበር የሚያመለክቱት መምህር ብርሀኑ፤ አሁን በመቅረቱ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል ባይ ናቸው፡፡ አዋሽ ከየት ተነስቶ  ወዴት እንደሚጓዝ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የት እንደሚገነባ የማያውቁ ሰዎች እንዳጋጠሟቸው ይጠቁማሉ፡፡ ሁኔታውን መቀየር እንዳለበትም ያመለክታሉ፡፡
ቀደምት የአገሪቱ መሪዎች የነበሩት አጼ ዮሐንስ የትግሬ፣ አጼ ቴዎድሮስ ጎንደሬ አጼ ምኒልክ የሸዋ የሚያደርጋቸው ነገር የለም፡፡ ለእኔ ሁሉም የእኛ ናቸው፡፡ መሪዎቹ ለአንደኛው ባለቤት ለሌላው ህዝብ ጎረቤት የሚሆኑበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ አሁን ትልቁ በሽታችን ይህ በመሆኑ መቀየር አለበት ይላሉ፡፡
ለምን የአጼ ዮሐንስ ሃውልት መቀሌ ላይ ብቻ ይሰራ ይባላል፡፡ ለምን ነቀምት ላይስ አይሰራም፡፡ የአጼ ቴዎድሮስ ሀውልትስ ለምን ጎንደር ይሰራል መቀሌ ላይ ለምን አይሰራም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ መሪዎች የኢትዮጵያ ነገስታት እንጂ የትግሬ፣ የጎንደር ወይም የሸዋ ንጉሶች አይደሉም መፈጠር ያለበትም የእኛ ናቸው የሚል ስሜት መሆን እንዳለበት ይከራከራሉ፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሒሩት ወልደ ማርያም፤ የአድዋ ድልን  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ክብር ማህተም፣ የጥቁር ህዝቦችና የቅኝ ግዛት ተጠቂ የነበሩ የመላው ዓለም ህዝቦች የነጻነት ተጋድሎ ቀንዲል፣ በእውነትና በፍትህ ህልውናና ምልአት ላይ ያረፈ ታላቅ ድል ሲሉ ይገልጹታል፡፡
በዓሉ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍን የከፈተ፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች ብሄር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖትና አካባቢ ሳይለያቸውና ሳይከፋፍላቸው በአንድነትና በጋራ  በመሆን ወራሪውን የጣሊያን ጦር ውርደት ያከናነቡበት እንደሆነም ያስታወሳሉ፡፡ የኢጣሊያን ወራሪ ጦር ዳግም ከ40 ዓመታት በኋላም ቂም ቋጥሮ፣ በበቀል ተነሳስቶ እና የበለጠ ዝግጅት አድርጎ ሲመለስ የአድዋ ድል ቅርስ፣ ውርስ እንዲሁም አቅም ሆኗቸው የማታ ማታ ድል አድርገው በድጋሚ አሳፍረው እንደመለሱም ያመለክታሉ፡፡
እንደ ዶክተር ሒሩት ማብራሪያ፤ የአድዋ ድል ከኢትዮጵያም አልፎ ለሌሎች ህዝቦች ታላቅ ታሪካዊ ትሩፋት ሆኖ አገልግሏል፡፡ አውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን የመቀራመት ህልማቸውንና ጅማሯቸው የማይቻል መሆኑን አስገንዝቧል፡፡ ሂደታቸው እንደማያዋጣም መርዶ የተረዱበት፣ ለአፍረካውያን ነፃነት የመጀመሪያው ደወል የተደወለበት ነው፡፡ ለሌሎች አፍሪካውያን ወንድሞችና እህቶች ከቀኝ ግዛት ነጻ ለመውጣት የይቻላል ጠንካራ መንፈስና እንደ ኢትዮጵያውያን የአድዋን ድል እንደ ቅርስና ውርስ ይዘውት ረጅምና መራራውን ትግላቸውን እንዲበረቱበት ያስቻላቸው  ነበር፡፡  
ከዚህ ባሻገርም ከአፍሪካም አልፎ በዓለም ላይ የነጭ የበላይነት፤ የጥቁር የበታችነት የተዛባ አመለካከት ሰፍኖ የቆየውን አስተሳሰብ የሰበረ፣ በተለያዩ ዓለም ክፍሎች ይኖሩ የነበሩ ጥቁር ህዝቦች  አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱ ያስቻለ አለም አቀፍ ድል እና የኩራት ምንጭ መሆኑንም ነው ዶክተር ሒሩት የሚናገሩት፡፡  
አድዋ በረጅም ታሪካዊ ሂደትና ማህበራዊ ትስስሮች የተገነቡ እሴቶች ውጤት መሆኑን የሚናገሩት ሚኒስትሯ፤ እሴቶቹ ለነጻነት መቆም፣ ከራስ አልፎ ለሌላው መስዋዕትን፣ ራስ አክባሪነትን እና በቀላሉ የማይናወጥ ጠንካራ ስነ ልቦና ባለቤትነትን ያካትታል ይላሉ፡፡ አብሮነት፣ ጀግንነት፣ ከግላዊነት ከፍ ያለ ስብዕና ባለቤትነት፣ መንፈ ሳዊነትን የሚያካትቱ ኢትዮጵያዊነት የተገነባበት የመሰረት ድንጋይ አካላት እንደሆኑ፣ እሴቶቹ ኢትዮጵያዊነት የተሰራበት ድርና ማግ እንዲሁም ማገር መሆናቸውንም ያክላሉ፡፡
በመሆኑም የአድዋን ድል ታሪክ ከነእሴቶቹ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የአድዋን ድል የጦርነት አውድ በታሪካዊ ቦታነቱ ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻና የጥናትና ምርምር ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ያመለክታሉ፡፡ የፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ፣ የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየምና አድዋን የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ ከተግባሮቹ መካከል ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ያመለክታሉ፡፡
122ኛው የአድዋ በዓል ‹‹አድዋ በአብሮነት የአሸናፊነት ተምሳሌት›› በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ መሆኑን የሚናገሩት ሚኒስትሯ፤ ትውልዱ የአገሩን አኩሪ ታሪክ በማስጠበቅ፣ የወቅቱ ጠላት የሆነውን ድህነትን፣ መከፋፈልን እና ሙስናን በማሸነፍ የአባቶቹንና የእናቶቹን የድል ታሪክ ለመድገም ቃል ሊገባ የሚገባበት ጊዜ ሊሆን እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡ ሀገሪቱ የጀመረችውን የልማትና የዕድገት ጉዞ ለማስቀጠል አድዋ ትልቅ የሞራል ስንቅ ሆኖ ሊያገለግል ይገባል ሲሉም ያሳስባሉ፡፡
እንደ ዶክተር ሂሩት ማብራሪያ፤ ኢትዮ ጵያውያን አድዋ ላይ ያሸነፉት በአንድነት፣ በትብብርና በጋራ ሆነው ነው፡፡ የዘመቱት ሃይማኖት፣ አካባቢ፣ ብሄር፣ ቋንቋ ሳይለያቸውና ሳይገድባቸው በህብረት ነው፡፡ የአሁኑ ትውልድም ከእዚህ ትምህርት ወስዶ የብሄርና የቋንቋ ክፍፍልና ከመሰል  አፍራሽ ተግባራት ራሱን ማራቅ ይጠበቅበታል፡፡ ተግባራቱ ሊያደርሱት የሚችሉትን ሀገራዊ ኪሳራ በመረዳትና በመገንዘብ አንድነቱን በማስጠበቅ የአገሩን ህልውና መጠበቅ ይገባዋል ሲሉም ይመክራሉ፡፡
የአገሪቱ ሉዓላዊነት ተጠብቆ አባይን በመሰሉ ወንዞችና ሌሎች የተፈጥሮ ሃብቶች ለማልማት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ለማስተጓጎል በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚደረጉ ጫናዎችና፣ የሚቃጡ ጥቃቶችን በንቃት መከታተልና መከላከል እንደሚገባም ያሳስባሉ፡፡ አድዋን ቅርስና አስተሳሰብ ዛሬም ትውልዱ ጥቅም ላይ በማዋል ሊኖርበት እንደሚገባም ይናገራሉ፡፡  
አድዋ የኢትዮጵያውያንና የመላ ጥቁር ህዝቦች አኩሪ የድል ታሪክ ነው፡፡ለቀጣዩ ትውልድም አሸናፊነትን መልዕክት ማስተላለፍ ይገባል የሚሉት ዶክተር ሂሩት፤ድሉ ሉዓላዊት ኢትዮጵያን በአለም ካርታ ያስቀመጠ አስገራሚ ክስተት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም ዛሬም የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ተሰሚነት እንዲከበርና እንዲያድግ ለሚደረገው ትግል ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር ቅርስ መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡  
የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦች ዘር፣ ቀለም፣ ቋንቋ እና አካባቢ ሳይወስናቸው ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በአንድነት በመንቀሳቀስ ኢትዮጵያዊነት፤ ህብረት፣ አብሮነት፣ መተባበር፣ ፍቅር፣ አልበገር ባይነትና ድል አድራጊነት መሆኑን ያረጋገጠ የህዝቦች ድል ነው፡፡ ይህም ሀገራዊ እሴቶችን እንድንጠቀምና እንድንጠብቅ ያበረታታል፡፡
ዶክተር ሂሩት፤ ድሉ የዓለምን ትኩረት መሳብ ያስቻለ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ የአድዋ ድል ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ማበብ ምክንያት ሆኗል። አገሪቱ በንቃት በምትሳተፍባቸው ኔፓድን በመሳሰሉ መርሀ ግብሮች አፍሪካን ከድህነት ለማውጣት፣ የሯሷን ጉዳይ በራሷ እንድትፈታ ለማስቻል የሚደረገውን የማይተካ ሚና ማጠናከር እንደሚገባም ያሳስባሉ፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ፤ አድዋ በአብሮነት የተገኘ የአሸናፊነት ተምሳሌት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹አድዋ የእኛ ድል ነው›› ሲሉም  በመተባበር የተገኘ ድል መሆኑን ይመሰክራሉ፡፡ የእኛ የሚለው ሃሳብ ወደፊት ብዙ ርቀት ለመጓዝ እንደሚረዳም ይናገራሉ፡፡ እኛነታችን ውስጥ አብሮነት መኖሩን ያስታውሰናል፤ አብሮነት አቅም ነው። በቀላሉ የማይረታ ትልቅ ሃብት ነው ይላሉ፡፡
እንደርሳቸው ገለጻ፤ አሸናፊነትን አላማ አድርጎ ለተነሳ ትውልድ አብሮነትን መንከባከብ ይገባዋል፡፡ አብሮነት የሚገኘውም በመደማመጥ፣ በመተማመን፣ በመከባበር እና በመፈቃቀር ነው፡፡ የአድዋ ድል እንደ አሁኑ ዘመን በርካታ የመገናኛ መንገዶች ባልነበሩበት ወቅት የተገኘ ነው፡፡መረጃ በስፋት ስለተነገረ ሳይሆን በውስን የተላለፈውን በመስማት፣በመደማመጥ፣ በመከባበርና በመተማመን የተገኘ ድል ነው፡፡
ዛሬ መረጃ በበዛበት ወቅት ለመረጃዎች የምንሰጣቸው ትርጉሞች ስለሚለያዩ አብሮነትን እየተሸረሸረ ይገኛል። በመሆኑም ትውልዱ መንቃት ይኖርበታል፡፡ድሉ የእኛ ነው ለማለት አንድነትን መገንባት እንደሚያስፈልግም ይመክራሉ፡፡ አንድነትን የሚገነባው በመደማመጥ፣ በመተማመን እና በመከባበር በመሆኑ ለእነዚህ ጉዳዮች ትኩረት መስጠት ይገባል፡፡            
የአሁኑ ትውልድ የተጋረጡ ጠላቶቹን ለይቶ ማወቅ ይጠበቅበታል፡፡ ጥላቶቹን የማያውቅ ከሆነ ራሱን ይጎዳል፡፡ ድህነትና ኋላቀርነት በትክክል ለተረዳው ትልቁ ጠላት ነው፡፡ ትውልዱ ይህ ከጫንቃው እንዳይወርድ የሚሰሩ አካላትንም ለይቶ ማወቅ፤ የውስጥ ችግሮቹን መፍታት ይገባዋል። አደዋ የአንድነት ውጤት ነው። ስለዚህ እንደ አደዋ ሁሉ ለሌሎች ድሎችም እንትጋ መልዕክታችን ነው።   

ዘላለም ግዛው  

Published in ፖለቲካ

ኢትዮጵያ፤ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶችን ከውጪ በማስገባት ከፍተኛ  የውጪ ምንዛሬ ታጣለች፡፡ በመሆኑም መንግስት ችግሩን በመፍታት የውጪ ምንዛሬን  ለማስቀረት  ግብአቶችን  በአገር ውስጥ ምርት መተካት ላይ ትኩረት አድርጎ   እየሰራ ይገኛል፡፡ ለዚህም የአገር ውስጥ ባለሃብቱ   ምርቶችን በማቅረብ ግንባር ቀደም ተዋናይ እንዲሆን  ድጋፍ እየተደረገለት ነው፡፡
ኤጂ ቧንቧ መገጣጠሚያ ቴክኖሎጂ   ሀላፊነቱ የተወሰነ  የግል ኩባንያ ከኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች  ኢንዱስትሪ  ልማት ኢንስቲትዩት ጋር ባዘጋጀው ወርክሾፕ  ለገበያ ባቀረባቸው አዳዲስ የቧንቧ ምርቶች ዙሪያ  ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል፡፡ በውይይቱ  ግብዓቶቹ በአገር ውስጥ መመረታቸው  የውጪ ምንዛሬን ከማስቀረት  ባሻገር አገሪቱ በምታደርገው የውኃ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ የሚታየውን የጊዜ መዘግየት ማስቀረት እንደሚቻል ተነስቷል፡፡      
የደቡብ ክልል ውኃና መስኖ ልማት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ነጋሽ  ዋጌሾ  እንደሚናገሩት፤ መንግስት የመጠጥ ውኃ መሰረተ ልማት ዝርጋታን በአገሪቱ  ለማዳረስ    ከወትሮው በተለየ መልኩ  በስፋት እየሰራ   ባለበት  በአሁኑ  ወቅት   ይሄንን  የሚያግዙ    የቧንቧ መገጣጠሚያ ምርቶች  በአገር ውስጥ ኩባንያዎች  ተመርተው መቅረባቸው  በጣም ወሳኝ ናቸው፡፡ ይህም ህብረተሰቡ  የቧንቧ  መገጣጠሚያ ምርቶቹን   በቅርበት እንዲያገኝ የሚያደርግና በግብዓት እጦት ምክንያት  የሚከሰተውን የውኃ መስመር ዝርጋታ መዘግየት  የሚያስቀር ነው፡፡
እንደ ዶክተር ነጋሽ ማብራሪያ፤ ዛሬ በአገር ውስጥ በባለሀብቶች ተመርተው ለገበያ   የቀረቡት የላስቲክ ቧንቧ መገጣጠሚያዎች  ከዚህ ቀደም  በውጪ አገር  ምንዛሬ  እየተገዙ ወደ አገር ውስጥ በከፍተኛ ገንዘብ የሚገቡ ናቸው፡፡ እነዚህ ግብዓቶች  በአገር ውስጥ መመረታቸው ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ፤ በሚፈልገው መጠን  እና አይነት እንዲያገኛቸው ያስችላል፡፡ ይህም በአገሪቱ  በውኃ  መሰረተ ልማት ግንባታ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ  ይበልጥ ወደ ፊት የሚያራምድ ይሆናል፡፡
አብዛኛውን ጊዜ ህብረተሰቡ  የቧንቧ መገጣጠሚያ ምርቶች  ግዢ ሲፈጽም   ትኩረት  የሚደረገው  የውጪ አገር  ምርት ላይ  እንደሆነ  የተናገሩት ዶክተር ነጋሽ፤ ሆኖም  ግን  በአገር ውስጥ  እየተመረቱ ያሉ ምርቶች፣ በጥራት ደረጃቸው፣ የአመራረት ዘይቤያቸው የዘመኑን ሳይንሳዊ ቴክኖሎጂን  ተጠቅመው የሚመረቱ በመሆናቸው የውጪ ምርቶችን  ሊተኩ  የሚችሉ ናቸው፡፡ ጥራታቸው ከውጭ ከሚገቡት  ምርት  የሚያንስ አይደለም፡፡
በመሆኑም ህብረተሰቡ ከዚህ በፊት ለአገር ውስጥ ምርት ያለውን  አመለካከት በመስበር ሊጠቀምባቸው ይገባል፡፡ ምርቱንም  በመጠቀምና  በመፈተሽ  ችግር ካለበት ለአምራቹ አካል በመንገር ኩባንያው  ራሱን እያሻሻለ እንዲሄድ ማገዝ  ይኖርበታል፡፡ ይሄም  በአገሪቱ ውስጥ የሚደረገውን  የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚደግፍ  ነው ብለዋል፡፡
‹‹አምራቹ በየጊዜው ራሱን   እያረመና እየፈተሸ ደረጃውን  የጠበቀ ምርት ማምረት  ይኖርበታል፡፡ በገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት አለበት፡፡ በአመራረት ዘይቤው ለጊዜው ብቻ ሳይሆን በዘለቄታው ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር መራመድና ምርቱም   ተጠቃሚው ጋር በሚደርስበት ወቅት ተከታትሎ ዋስትና ሊሰጥ ይገባዋል›› ብለዋል ዶክተር ነጋሽ፡፡  
በመንግስት ደረጃ ሊሸፈኑ በማይችሉ  የልማት ሥራዎችና   የገበያ ክፍተት ባለባቸው የኢንዱስትሪ ግብዓቶች  ምርት ላይ   በሽርክና ማህበር ይሁን  በግል ሥራ ላይ  መስራት ለሚፈልጉ   ድርጅቶች  መንግስት  እያበረታታ እንደሚገኝ  የተናገሩት ዶክተር ነጋሽ፤ በመሆኑም የግል ባለሀብቶችም ይሁን በሽርክና ማህበር የተደራጁ አካላት  ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን  በአገር ውስጥ በመተካት በኩል   ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው፡፡ አዳዲስ ሊያሰሩ የሚችሉ ሀሳቦችን ማመንጨትና ወደ ሥራ መግባት ይኖርባቸዋል፡፡ ዛሬ ላይ በአማራ ክልል የተጀመረው የቧንቧ መገጣጠሚያ ቴክኖሎጂ ወደ ተለያዩ  የአገሪቱ ክፍል ቅርንጫፉን  በማስፋት ተደራሽ መሆን ይኖርበታል፡፡ ኩባንያው በአገሪቱ ገበያ ውስጥ   ያለውን እጥረት በማስወገድ የቧንቧ መገጣጠሚያ ምርቶችን  በሥፋት በማምረት ማከፋፈልና ችግሩን በመፍታት በኩል ይበልጥ መስራት ይኖርበታል፡፡ ህብረተሰቡ ውስጥ ዘልቆ በመግባት ስለምርቶቹ  ግንዛቤ መፍጠር  ያስፈልጋል  ብለዋል፡፡
የኤጂ ቧንቧ መገጣጠሚያ  ቴክኖሎጂ  ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ  አቶ አቻ ደምሴ፤ በበኩላቸው  ኩባንያው ለመስኖ ዝርጋታ፣ ለመጠጥ ውኃ፣ ለአበባ ምርትና ለኮንስትራክሽን አገልግሎት የሚውሉ የቧንቧ መገጣጠሚያ ምርቶችን  እንደሚያቀርብ ይናገራሉ፡፡ የቧንቧ መገጣጠሚያ ምርቶቹ  የየራሳቸው ቅርጽ፣መጠንና ይዘት አላቸው፡፡ምርቶቹ ከዚህ ቀደም ከውጪ አገር የሚገቡ ከመሆናቸውም   አንጻር   በአገር ውስጥ   ማምረት መቻላቸው በዘርፉ ያለውን  የገበያ ክፍተት በተወሰነ መንገድ  ለመፍታት  የሚያስችሉ ናቸው፡፡ ሆኖም  ግን አገሪቱ ከምትፈልገው የቧንቧ መገጣጠሚያ ምርቶች  አንጻር  በቂ  ባለመሆኑ ብዙ መስራትን ይጠይቃል፡፡     
ኩባንያው የቧንቧ መገጣጠሚያ ምርቶችን  ለማምረት  ጥሬ እቃ  ከውጪ አገር እንደሚያስመጣ የተናገሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ ግዢው  ከፍተኛ ዶላር  የሚጠይቅ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ   የውጪ ምንዛሬ  ከፍተኛ ተጽዕኖ  እያደረገ ይገኛል፡፡ሆኖም ችግሩ ሊፈታ አልቻለም፡፡ ስለዚህ ችግሩን ለመፍታት  ከመንግስት ከፍተኛ ድጋፍ  ያስፈልገናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡    
አቶ አቻ እንደሚሉት፤ ኩባንያው በተጠናከር መልኩ ወደ ሥራ ለመግባት የሰለጠነ የሰው ሀይል ያስፈልገዋል፡፡ ምርቶቹ ላይ ግንዛቤ ባለመፈጠሩ የገበያ ትስስር  ክፍተት አለ፡፡ ‹‹ኩባንያው በተደራጀ አቅም  ወደ  ሥራ መግባት ከቻለ ለዜጎች  የሥራ እድል ፈጠራ፤ አገሪቱ የጀመረችው የልማት ጉዞ ለማሳደግ ሚናው የጎላ ነው፡፡ወርክሾፑ መካሄዱ  በቀጣይ  ኩባንያው  የገበያ ትስስር እንዲፈጠርለት ያግዘዋል፡፡ የተጨማሪ የሥራ እድል እንዲፈጠርም አስተዋፅኦ ይኖረዋል›› ብለዋል፡፡
የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች  ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት  ዋና ዳይሬክተር  አቶ ሳሙኤል ሀላላ በበኩላቸው፤  የአለም ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነቱ የሚለካው  ብቃት ያለው የሰው ሀይል ሲኖረው በመሆኑ   ኢንስቲትዩቱ ብቃት  ያለው የሰው ሀይል  ለማፍራት ከኩባንያዎቹ ጋር በመሆን  የተለያዩ ሥልጠናዎችን  እየሰጠ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡ ሥልጠናው  ከውጪ አገር  በመጡ ባለሙያዎች የታገዘ ነው፡፡
የአገር ውስጥ ምርትን ለማምረት ማሽነሪዎችን በየደረጃው መግዛት ይቻላል ያሉት ዳይሬክተሩ ሆኖም ግን  በማሽኑ ልክ የሚሰራ የሰው ሀይል ያስፈልጋል፡፡ምክንያቱም የተወዳዳሪነት ዋናውና ቁልፉ መሳሪያና ብቃት ያለው የሰው ሀይል  ነው፡፡ በዚህም  ረገድ ኢንስቲትዩቱ  ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ፡፡  
እንደ አቶ ሳሙኤል ገለፃ፤ከውጪ ምንዛሬ ጋር ተያይዞ ለተከሰተው ችግር   በአገር ደረጃ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች  ቅድሚያ  እንዲሰጥ  ተደርጓል፡፡ በዚህም  ቀደም ብሎ በመንግስት ባንኮች ላይ ብቻ  መሰረት ተደርጎ ይሰጥ የነበረው የውጪ ምንዛሬ  አገልግሎት  አሁን የግል ባንኮች ጭምር ከሚሰበስቧቸው የውጪ ምንዛሬ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው  ቅድሚያ እንዲሰጡ የሚያስገድድ  ህግ  ወጥቷል፡፡ በዚህም የምንዛሬ እጥረቱን ለመፍታት እየተሰራ ነው፡፡
ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው የሥራ እድል ይፈጥራል፡፡ በውስጥ የቴክኖሎጂ አቅምን ይገነባል፡፡ በዚህም  የአገሪቱን የኢኮኖሚ ሽግግር አጀንዳን  በመሰረታዊነት ለማሳካት የሚሰራ አንኳር ዘርፍ ነው›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ  ለዚህም  ኢንዱ ስትሪው በተሟላ መልኩ የውጪ ምንዛሬ  ማነቆውን  ለመፍታትና  ለመደገፍ  መንግስት የሚያገኘውን  ማንኛውንም የውጪ ምንዛሬ በተሻለ መልኩ ለዘርፉ እያዋለ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
 ከዚህም ባሻገር ኢንዱስትሪዎች በራሳቸው አቅም የውጪ ምንዛሬን እንዲያመነጩ   አቅማቸውን  ማሳደግ ይጠይቃል፡፡ ይሄንን  ማድረግ  የሚቻለው ደግሞ  ተወዳዳሪ የሆነ ማኑፋክቸሪንግ   ኢንዱስትሪ መፍጠር ከተቻለ  ነው፡፡በአለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ መውጣት ከተቻለ የውጪ አገራት  ምርታቸውን  ኢትዮጵያ ልከው እንደሚሸጡ  ኢትዮጵያም ወደ ውጪ አገር በመላክ  የውጪ ምንዛሬ የማታገኝበት ምክንያት የለም፡፡ ኢንዱስትሪዎቹ ለዚህ ደረጃ እንዲደርሱ ማበረታታት ይገባል፡፡ በዚህም ብዙ ኢንዱስትሪዎች መጠናቸው ይነስ እንጂ ምርቶችን ወደ ውጪ ለመላክ ጥረት እያደረጉ ናቸው ብለዋል፡፡
 በገበያ ላይ  የቧንቧ  መገጣጠሚያ ምርቶች እጥረት አለ። ምርቶቹ በአገር ውስጥ መመረታቸው አገሪቱ ለምትገነባቸው የውኃ ልማት መሰረተ ልማቶች የጎላ ፋይዳ አላቸው፡፡ አገሪቱ በዘርፉ የምታወጣውን የውጪ ምንዛሬ የሚያድን በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል። ተያያዥ ችግሮች እንዲወገዱም በትብብር መስራት አስፈላጊ ይሆናል።

 ሰብስቤ ኃይሉ

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።