Items filtered by date: Sunday, 04 March 2018

አዲስ አበባ፦ ስድስት አገራትን ያሳተፈው አፍሪካን ሰርከስ ፌስቲቫል በኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ተካሄደ። በፌስቲቫሉ ላይ አስራ አንድ የሰርከስ ትርኢት የቡድን አባላት ተሳታፊ ሆነዋል። ሦስት ቀናትን የቆየው ፌስቲቫል ዛሬ ተጠናቋል።
የካቲት 23 ቀን በመኮንኖች ክበብ የተጀመ ረውን የሰርከስ ፌስቲቫሉን አስመልክቶ ከአዘጋጆቹ ጋር በተባባሪነት የተሳተፉት የአውሮፓ ኀብረት የአዲስ አበባ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ሚስስ ስቴሪ ሌክቲደን እንደተናገሩት፤ የተለያየ ባህል እና ክህሎት ያላቸው የአፍሪካ አገራትን ለማቀራረብ ይህን መሰሉን የሰርከስ ትርዒት ማዘጋጀቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ተናግረዋል። አሁን አሁን የሰርከስ ጥበብ በመላው ዓለም ላይ እየተስፋፋ በመምጣቱ ባህላቸው እና አኗኗራቸው የተለያዩ ህዝቦችን ለተሻለ ዓላማ እንደሚያቀራርብ ጠቁመዋል።
እንደ ሚስስ ስቴሪ ገለፃ፤ ለሁለተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ የተዘጋጀው ፌስቲቫል በሰርከስ ጥበብ ላይ ልዩ ብቃት ያላቸው ወጣት አፍሪካውያን ለማገዝ ሰፊ ዕድል ይከፍታል። በሌላ በኩል በአፍሪካ ሰላም ያለው ጠቀሜታ ለማስገንዘብ ሚናው ከፍተኛ ነው። የአፍሪካውያን የሰርከስ ትርኢት ለቀሪው ዓለም ለማስተዋወቅ እና ዘርፉን በተገቢው መንገድ ለማሳደግም ይህን መሰል ፌስቲቫሎች መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። በቀጣይም የአውሮፓ ህብረት በዚህ ዝግጅት ላይ ተባባሪ እንደሚሆን ቃልገብተዋል።
የሰርከስ ደብረ ብርሃን ኤክሲኩቲቭ እና አርቲስቲክ ዳይሬክተር ተክሉ አሻግሬ በበኩሉ፤ ከአፍሪካ አገራት ጋር ሰፊ የልምድ ልውውጥ በሚደረግበት የሰርከስ ፌስቲቫል ላይ ተጋባዣ መሆናቸው ትልቅ ዕድል መሆኑን አስታውሶ፤ ከዚያም ባለፈ መድረክ ላይ ሥራዎችን በማቅረብ ሰርከስ ያለውን ጥበብ እና የማቀራረብ አቅም ማሳየት የሚቻልበት፤ ለአንድነት፣ ለሰላም፣ ለባህል ብዝሀነት እና የዓለም አቀፍ ትብብርን በገሀድ ማሳየት እንደሚያስችል ጠቁሟል።
ፌስቲቫሉን ለሁለተኛ ጊዜ ያዘጋጀው የፍካት ሰርከስ ቡድን የኮሙኒኬሽን ባለሙያ ወይዘሪት ፍፁም አበራ እንደገለፀችው፤ 30 አባላት ያሉት የሰርከስ ቡድኑ በአገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ትርኢቶችን ያቀርባል። አሁን ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ የአፍሪካን ሰርከስ ፌስቲቫልን አሰናድቷል። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2009 ጀምሮ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሚገኘው የህፃናት ህክምና ማዕከል (ፔዲያትሪክ ሆስፒታል) ትርኢቱን አቅርቧል።
ባለፈው ዓርብ በድምቀት የተከፈተው አፍሪካን ሰርከስ ፌስቲቫል ከሞሮኮ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያ፣ ከሞዛምቢክ፣ ከደቡብ አፍሪካና ጊኒ የተውጣጡ 11 የሰርከስ ቡድን አባላትን እንዳሳተፈ የዝግጅት ክፍላችን ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ዳግም ከበደ

Published in የሀገር ውስጥ

ክብር አድዋ- ከምኒልክ አደባባይ እስከ እንጦጦ
«ባዶ እግር» በሚል ስያሜ ነው የተካሄደው፤ በሰውኛ ፕሮዳክሽንና ኢንተርቴይንመንት የተዘጋጀው የክብር አድዋ ዝግጅት። የአድዋ ድል በዓል በአዲስ አበባ በደማቅ ሁኔታ ከሚከበርበት የምኒልክ አደባባይ ጀምሮ እስከ አድዋ ድልድይ ድረስ በባዶ እግር የተደረገ ጉዞ ነው። ተጓዦችም በአደባባዩ ተሳታፊ ከሆኑ በኋላ፤ በአገር ባህል አልባሳት ደምቀው፤ አርበኞች ይዘው፤ ፊትአውራሪዎች በፈረስ ላይ ሆነው ጉዟቸውን ወደ አድዋ ድልድይ አድርገዋል።
በዚህ የባዶ እግር ጉዞ ከ2500 እስከ 3000 ሰዎች በደንብ አልባሳት ለብሰው በመርሐ ግብሩ ላይ ታድመዋል ተብሏል። ይህም በተናጠል በቻ ሳይሆን ከጎንደር የመጣ ቡድን፣ የቡና የእግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች ማኅበር፣ሮተሪ ኢንተርናሽናል፣ ኢትዮጵያ እይታዊ ጥበብ ወዳጆች ማኅበርና ሌሎችም በቡድን የመጡ መኖራቸው ታውቋል።
ጉዞው አድዋ ድልድይ ላይ እንደደረሰ በስፍራው የተገኙ ወጣቶች ለመንገደኞቹ ውሃ በማቅረብ ያስተናገዱ ሲሆን፣ ከአድዋ አደባባይ ጉዞ ወደ እንጦጦ ሆኗል። እንጦጦ በሚገኘው የምኒልክ ቤተመንግሥት ግብር ተበላ፤ ቴአትርን ጨምሮ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶች ቀረቡ። በዚህም 2ሺ የሚደርሱ ታዳሚያን ነበሩ።
በባዶ እግር ጉዞ ላይ የበገና እና የመሰንቆ ዜማዎች ቀርበዋል። ነጋሪት የሚጎስሙ 15 ወጣቶች በዓሉን ያደመቁት ሲሆን፣ ካህናትና መነኮሳት ተሳትፈዋል። ይህንንም የጎዳና ላይ ትርዒት ለማሳካትና ጉዞውም የተቃና ለማድረግ ለተባበሩ፤ ዝግጅቱንም ላደመቁ ጣይቱ ሆቴልን ጨምሮ የኢትዮጵያ እይታዊ ጥበባት ወዳጆች ማኅበር፣ ግጥምን በጃዝ፣ ኤንቲኦ አስጎብኚ እና ሌሎች ተቋማት ምስጋና ይድረስ ብለዋል፤ አዘጋጆቹ። ይህንንም መረጃ የክብር አድዋ ፕሮጀክት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮናታን ጠለለው አድርሶናል።
አድዋ በምኒልክ አደባባይ
የካቲት 23 ቀን 2010ዓ.ም እለተ ዓርብ ዋለ፤ የአድዋ ድል በዓል። ማለዳ ላይ 21 ጊዜ መድፍ ተተኮሰ። 122ኛውን የአድዋን ድል በዓል ለማክበር።በአዲስ አበባ ከተማ በዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ሐውልት ስር አርበኞችም በማለዳው ነው የተሰባሰቡት።
ወጣቶች፣ የኢትዮጵያ ስካውት ማኅበር አባላት፣ ተማሪዎች በስፍራው ታድመዋል። የኪነጥበብ ባለሙያዎችም አርበኞችን መስለውና ሆነው በመሸለልና በመፎከር የተለያዩ ትርኢቶችን አቅርበዋል። የመከላከያ ሠራዊት እንዲሁም የፌዴራል ፖሊስ ማርቺንግ ባንድ በአደባባዩ ዙሪያ የተለያዩ ዜማዎችን አስደምጠዋል። በስፍራው የታደመው የአዲስ አበባ ነዋሪ ከወትሮው የተለየ እንደነበር በስፍራው ተግኝተን አስተውለናል።
አድዋ ድል በሶሎዳ ተራራ ስር
የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በአድዋ ከተማ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል። ይህም «አድዋ በአብሮነት የአሸናፊነት ተምሳሌት» የሚል መሪ ሃሳብ የያዘ ሲሆን አድዋ ከተማ በብዛት እንግዶች ጎብኝተዋታልና ሽር ጉድ ብላ አስተናግዳለች።
በበዓሉ ዋዜማ ሐሙስ የካቲት 22 ቀን 2010ዓ.ም ዓውደጥናት የተካሄደ ሲሆን፤ በፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ የአድዋ ድልን ፋይዳ በተመለከተ ጥናታዊ ወረቀት ቀርቧል። በተጨማሪ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ አድዋና አካባቢውን ለማልማት ስለተያዘው አድዋ ተራሮችና የአድዋ ጦርነት ድል ቱሪዝም ፕሮጀክት ገለጻ ተደርጓል፤ በቀረቡት ጽሑፎች ላይም ውይይት ተደርጓል።
በስፍራው የመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ሙዚቃ ቡድን እና የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ ማርቺንግ ባንድ አባላት ጥዑመ ዜማዎችን አሰምተዋል፤ የአድዋ ወጣቶችም ትርዒቶችን ያሳዩ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አባላት በተመሳሳይ ሙዚቃዊ ቴአትር አቅርበዋል።
በእለቱ 260 ሚሊዮን ብር በጀት የተያዘለትና በሦስት ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለለት የአድዋ ተራሮችና የአድዋ ጦርነት ድል ቱሪዝም ፕሮጀክት ይፋ ሆኗል። ጦርነቱ የተደረገባቸው ሰንሰለታማ ተራሮች እና የጦር አውድማዎች ተጎብኝተዋል። በጉብኝቱ ከተለያዩ የግል እና የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን የተውጣጡ ከ40 በላይ ጋዜጠኞች የተሳተፉ ሲሆን፤ አርበኞች እና የኪነጥበብ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
በስፍራው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ተገኝተዋል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሒሩት ወልደማርያም (ዶክተር) ንግግር አድርገዋል። በዛም «የድካም ስሜት ሲሰማን የአድዋን ድል በማስታወስ ለሌላ አንፀባራቂ ድል መዘጋጀትና መትጋት ይጠበቅብ ናልም» ብለዋል።
ከአዲስ አባባ ከተማ በመነሳት ላለፉት አርባ አምስት ቀናት በእግር ተጉዘው አድዋ ከተማ የደረሱት «የጉዞ አድዋ አባላት» ዝግጅቱ ላይ ተገኝተዋል። ይህም የተለየና ደማቅ ስሜት የፈጠረ እንደነበር የተለያዩ የዜና ምንጮችን ጨምሮ በስፍራው የተገኙ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ባልደረባ መረጃውን አድርሰውናል።
አድዋ ድል- ከአንጎለላ-ሊቼ-አንኮበር
መገዘዝ መልቲ ሚድያ እና የቴአትር ፕሮዳክሽን፤ ከአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን የቴሌቪዥን ድርጅት ጋር በመተባበር የአድዋ ድል በዓል አክብሯል። ከየካቲት 16 ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች የተከበረ ሲሆን፤ በዋናነትም በዓሉ የተከበረው ዳግማዊ አጼ ምኒልክ እንዲሁም የአድዋው አርበኛ ፊት አውራሪ ገበየሁ የትውልድ ሥፍራ በሆነችው አንጎለላ ነበር። ታዳሚውም በአካባቢው ያሉ ታሪካዊ ስፍራዎች ተጎብኝተዋል።
ክብረ በዓሉ ቀጥሎ በማግስቱ ወደ አንኮበር ሄደዋል። ያም የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ቤተመንግሥት የሚገኝበት ነው። በአንኮበር ሎጅ በተካሄደው በዚህ ዝግጅት ጉብኝትን ጨምሮ የተለያዩ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶች ቀርበዋል። ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቧል፤ በክራር ጨዋታም ታጅቧል።
ከአዲስ አበባ ከናዝሬት እና ከሌሎች አካባቢዎች ተነስተው ወደስፍራው የሄዱትንም እንግዶች የአካባቢው ነዋሪ አድዋን ጉዞ በሚያስታውስ መልኩ ነጋሪት እየጎሰሙ፣ መለከት እየነፉ፣ ጋሻ ጦር ጎራዴ ይዘው እየሸለሉ ነው የተቀበሉት። በአንዷለም አባተ ተደርሶ የተዘጋጀ ሃያ ደቂቃ ርዝማኔ ያለው «የምኒልክ መስኮት» በሚል ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ለስልጣኔ ባበረከቱት አስተዋጽኦ ያጋጠማቸውን ተግዳሮቶች የሚያሳይና እንዴት በጥበብ እንዳለፉት የሚያስቃኝ ቴአትር ቀርቧል።
ጉዞው ቀጥሎ ወደ ሊቼ አምርቷል፤ አጼ ምኒልክ እና አጼ ዮሐንስ ስምምነትና ለእርቅ የተፈራረሙበት ስፍራ ነው። ይህም ቦታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የተጎበኘ ሲሆን፣ በተጨማሪ የታዋቂው የጦር አበጋዝ የበዛብህ የመቃብር ስፍራ ተጎብኝቷል። በዚህ በዓል በሦስቱም ቀናት በርካታ ሰዎች መታደማቸውን የቴአትር ባለሙያው ገጣሚና ደራሲ አንዷለም አባተ አድርሶናል።
ደራሲ አንዷለም አባተ (የአፀደ ልጅ) የመገዘዝ መልቲ ሚድያ እና የቴአትር ፕሮዳክሽን ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ጨምሮ እንደነገረን፤ አንጎለላ-ሊቼ እና አንኮበርና አካባቢውን ትልቅ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ፍላጎት አለ። ይህንንም እውን ለማድረግ ከዞኑ ባህልና ቱሪዝም ጋር እየተነጋገርን ነው ብሏል።

ዜና ሀተታ
ሊድያ ተስፋዬ

Published in የሀገር ውስጥ

ቋራ ላይ የተነሳው የአፄ ቴዎድሮስ የህይወት ጉዞ በመቅደላ ተፈጽሟል።ንጉሱ ከጎንደር በኋላ የሥልጣን ማዕከላቸውን ለጊዜው ወደ ደብረ ታቦር ከዚያም ወደመቅደላ በማዞር ቤተመንግሥታቸውን ገንብተዋል። በወቅቱም ንጉሱ መቅደላ አምባን በኢትዮጵያ የሚገኙ በርካታ ቅርሶች አሰባስበው ያኖሩበት ቦታ ነበር። 

በአምባው ላይ ቀደምት የዓለምን ሳይንስ የሚመራመሩና ጥልቅ ሃሳብ ያላቸው መጽሐፍት፣ የወርቅና የብር መገልገያዎች፣ አክሊሎችና ሌሎች የአገሪቷ ውድ ቅርሶች ሁሉ በአንድነት እንደነበሩበት ታሪክ ያስረዳል። በአፄ ቴዎድሮስ እና በእንግሊዞች መካከል በተደረገው የመቅደላው ጦርነት ላይ ንጉሱ እጅ አልሰጥም ብለው ሽጉጣቸውን ጠጥተው አርፈዋል። ከዚህ በኋላ ግን በጄኔራል ናፒዬር የተመራው የእንግሊዝ ሠራዊት ቦታውን ተቆጣጥሮ የኢትዮጵያን ቅርሶች መዘበራቸው። ጄኔራል ናፒዬርም እነዚያን ውድ የአገሪቷን ሃብቶች በበቅሎና በግመል አስጭኖ አገሩ ገባ።  አብዛኛዎቹ ንብረቶች በእንግሊዝ ቤተመጽሐፍት እና ሙዚየሞች ይገኛሉ። በአሁኑ ጊዜም ከንጉሠ ነገሥቱ አናት ላይ የተሸለተውን ሹሩባ ፀጉር ጨምሮ ሌሎች ቅርሶች በእንግሊዝ አገር የተለያዩ የሥነ-ቅርስ መዘክሮች ውስጥ በመጎብኘት ላይ ናቸው። በወቅቱ እንግሊዞች ድል ማድረጋቸውን ለአገራቸው ህዝብ ለማሳየት አፄ ቴዎድሮስን በህይወት ይዘው ለመሄድ አስበው ነበር። ግን በንጉሱ እጅ አልሰጥም ባይነት ሳይሳካ ቀርቷል። ምርኮ መውሰድ የፈለጉት እንግሊዞችም በዚህ ምትክ የንጉሱን ልጅ አለማየሁ ቴዎድሮስን ወደ አገራቸው እንደወሰዱ ታሪክ ምስክር ነው። ለመሆኑ ደጃዝማች አለማየሁ እንዴት ወደ እንግሊዝ አገር ሄደ? ኢትዮጵያስ ቅርሶችን ከማስመለስ አንጻር ምን ያህል ተሄዶበታል? በሚለው ጉዳይ ላይ የተለያዩ ምሁራን ሃሳባቸውን ያጋራሉ።
የወሎ ዩኒቨርሲቲው የታሪክ ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ጋሻው መሃመድ እንደሚሉት፤ መቅደላ ላይ የተዘረፉት የኢትዮጵያ ሃብቶች በርካታ ናቸው። መቅደላ በወቅቱ የአገሪቷ የቤተመጽሐፍት ማዕከል፣ የግምጃ ቤት ማዕከል እና ቤተመንግሥት በመሆኗ በዓለም ላይ ተመሳሳይነት የሌላቸው መጽሐፍት እና የአገሪቷ ቅርሶች መከማቻ ቦታ ነበር። ስለሆነም እንግሊዝ አብዛኛውን የኢትዮጵያ ቅርስ መውሰዷን ያረጋግጣል። ሰፊ ጥናት እና ምርምር በማካሄድ የቅርሶቹን ዓይነት እና ብዛት በመመረመር በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ማስመለስ ያስፈልጋል። ከዚህ ውስጥ አንዱ የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ አለማየሁ ቴዎድሮስ እንደሚገኝበት ይናገራሉ።
እንደ ረዳት ፕሮፌሰር ጋሻው ገለጻ፤ አጽሙን ለቅርስነት ማስመለስ ያስፈልጋል በሚለው ሃሳብ ላይ በአንድ ወገን ኢትዮጵያ የንጉሱን ልጅ እንደቅርስነት ልትጠቀምበት እና ገቢም ልታገኝበት ይገባል የሚሉ ወገኖች ቢኖሩም አለማየሁ ምን ታሪክ ሰርቷል ሊታወስ ብዙም አይገባውም የሚሉ ወገኖች መፈጠራቸው ግን አግባብ አይደለም ይላሉ። የሚከበር ሰው እንኳንም ከውጭ አገር ይቅርና በአገር ውስጥም አጽሙ ተነስቶ በሚገባ ቦታ ይቀበራል። ቅርሱ ቢመጣ ደግሞ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ፋይዳ ይኖረዋል። በተለይ ለአዲሱ ትውልድ አዕምሮ ውስጥ ስለአገር ፍቅር እና አንድነት እንዲሁም ስለማንነት የሚሰጠው መልዕክት ያይላል። በመሆኑም ቅርስ አያስፈልግም ብሎ መቀመጥ ተገቢ አለመሆኑን ይናገራሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አቶ አበባው አያሌው በበኩላቸው፤ የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ እንግሊዞች ልዑል እያሉ ቢጠሯቸውም ትክክለኛ መጠሪያቸው ደጃዝማች አለማየሁ ነው። ከአገሩ ሲወጣ የአስር ዓመት ልጅ ነበር። እንግሊዞችን መቅደላ ላይ ካሸነፉ በኋላ እነጄኔራል ናፒዬር ልጁን በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን የተማረሩ ሰዎች ይገድሉታል በሚል ሃሳብ ወደ አገራቸው እንደወሰዷቸውም መረጃዎችን ሲያገላብጡ እንደተመለከቱ ይናገራሉ። በተጨማሪም ደጃዝማች አለማየሁ ከንጉሱ ህጋዊ ሚስት የተወለዱ በመሆኑ እንግሊዞችም በምርኮነት እና እናታቸው የደጃች ውቤ ልጅ እቴጌ ጥሩወርቅ በምርኮ ጉዞ ወቅት መንገድ ላይ ስለሞቱ የእንግሊዙ ካፒቴን እስፒዲ በሞግዚትነት ተቀብሎ አገሩ ይዞት ገብቷል።
ዘረኝነት በተንሰራፋበት እና ጥቁር በሚጠላላበት ዘመን አለማየሁ የሚደርስበትን መጥፎ የስነልቦና ጫና መገመት ያስፈልጋል የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር አቶ አበባው፤ የስጋ ምቾች ባይጓደልበትም የመንፈስ ምቾት ግን አሰቃይቶታል። ከበሽታ ይልቅም ብቸኝነት እና የአገሩ ናፍቆት ለሞት አብቅቶታል። የልብ ጓደኛ ማጣት እና በማያውቀው ህብረተሰብ ውስጥ በልጅነት መኖሩ ህይወቱን ፈታኝ ማድረጉ ይታመናል። ነገር ግን እንግሊዞች ክብር ሰጥተው መቃብሩ ላይ ሐውልት ማቆማቸው ብቻ በቂ ነው። ከዚህ ውጪ ኢትዮጵያ ውስጥ የልጅ አለማየሁ ብሎ መዘከር እና እንደቅርስ መቁጠር አይገባም። ምክንያቱም የንጉስ ልጅ ከመሆኑ ውጪ ያን ያህል ገኖ የሚታይ ታሪክ የለውም። ልጁ ህይወቱ ቢያሳዝንም ታሪክ ላልሰራ ሰው መዘከሩ አይዋጥልኝም ይላሉ።
ያም ሆነ ይህ ግን የቅርስ ትንሽ ትልቅ የለውም ሁሉም በአግባቡ ከተሰራበት ለአገር ሃብት እና አንድነት ምንጭ መሆን ይችላል። የጳውሎስ ኞኞ አፄ ቴዎድሮስ መጽሐፍ አለማየሁ በእንግሊዝ አገር በጠና ታሞ ህዳር 5 ቀን 1872 ዓ.ም በተወለደ በ19 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለየ ያስነብባል። በንግስት ቪክቶሪያ ትዕዛዝ ዊንድሠር በሚገኘው የነገሥታት መቀበሪያ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን መቀበሩንና በመቃብሩም ላይ «እንግዳ ሆኜ መጣሁ ተቀበላችሁኝ» የሚል ቃል መስፈሩን ይሄው መጽሐፍ ይገልፃል።

ዜና ሀተታ
ጌትነት ተስፋማርያም

 

Published in የሀገር ውስጥ

ሀገራችን የፈጠራ ባለሙያዎችን በየዓመቱ ትሸልማለች፤ ለሥራቸውም የአዕምራዊ ንብረት የባለቤትነት መብት (የፓተንት ራይት) ትሰጣለች። በአንፃሩ ደግሞ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት አበርክቶ እንዲያደርጉ ከማገዝ አንጻር ውጤታማ ሥራ እንዳልሰራች ትታማለች። ለምን ይሆን? 

ወጣት ዮሐንስ ኪዳኔ በ2006 ዓ.ም በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ሙያተኞች ሥራዎቻቸውን ማህበረሰቡ እንዲያውቅ ለማድረግ የሚያስችል የመረጃ አገልግሎት ማሰራጫ ዘዴን በመፍጠር ተሸላሚ ነው። በ2009ዓ.ም ደግሞ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ የሚስተዋለውን የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ሊያሻሽል የሚችል የፈጠራ ሥራ በመሥራቱም ተሸልሟል። በፈጠራ ሥራ ተሰማርተው ለሽልማት የሚበቁ በርካታ ሰዎች ፈጠራቸው ከእውቅና ወረቀት የዘለለ ሥራ እንዲሰራ እየተደረገ አይደለም። በተለይ የመንግሥት እገዛ ሸለምኩና የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰጠሁ ከማለት ውጪ ወደ ተግባር የመቀየሩ ሥራ እንዳልተከናወነ ይገልጻል።
ፈጠራ የሰራውን መሸለምና የፈጠራ ባለቤትነት መብት መሥጠት፤ የፈጠራ ባለሙያውንም ሆነ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚሆንበት መንገድ መዘርጋት ነው። ነገር ግን በመንግሥት ተቋማት እንደ ግብ ተደርጎ እየተወሰደ በመሆኑ የፈጠራ ባለሙያዎቹ በሥራቸው ውጤታማና ኢኮኖሚውን እንዲደግፉ አልተደረገም። ተስፋ በመቁረጥ «ባልሰራስ» የሚል አስተሳሰብ እየተፈጠረ እንደሆነ ወጣት ዮሐንስ ያስረዳል። የገቢ ምንጩ የፈጠረው ሥራ እንዲሆን የሚያስችልበት ቁመና ላይ ስላልደረሰ በሌላ ሥራ ነው ኑሮውን የሚደጉመው።
የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት የፓተንት ጥበቃና ቴክኖሎጂ ሽግግር ክፍል ዋና የሥራ ሂደት አቶ ፍቅረ ተስፋዬ እንደገለጹት፤ የፈጠራ ባለሙያዎች እንዲበረታቱ የሚፈለግበት ዋና ዓላማ ሳይንስና ቴክኖሎጂን አሳድጎ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ነው። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ የፈጠራ ባለሙያዎች ለስም ብሎ ማድረግ እስኪመስል ድረስ የፈጠራ ባለቤትነቱን ካገኙ በኋላ እንደማይሰሩበት ይናገራሉ። የፈጠራ ሥራውን የማንቀሳቀስና ገንዘብ እንዲያስገኝ የማድረጉ ሁኔታ መጀመር ያለበት ከእነርሱ ነው። ይህ መሆኑን ቢረዱም ግን መሥራት አይፈልጉም። ስለዚህ በብዙዎች ዘንድ የፈጠራ ውጤቱ ወደ ቢዝነስ አለመቀየሩ አገሪቱን እንዳይጠቅም ከማድረጉም በላይ እራሳቸውም እንዳይለወጡ እንቅፋት ሆኖባቸዋል።
በፈጠራ ባለሙያዎችና ባለሀብቶች መካከል ያለ መስተጋብር ላይ በትኩረት አለመሰራቱ፣ ህግና ፖሊሲ በጉዳዩ ዙሪያ አለመውጣቱና ቴክኖሎጂንና የፈጠራ ባለሙያዎችን ተጠቅሞ ገንዘብ የማግኘት ልምዱ ያለመዳበሩ ክፍተቶች እንዲፈጠሩ አድርጓል።
በሳይንስና ቴክኖሎጂ የምርምርና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሹመቴ ግዛው፤ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሽልማቶችን ሲያደርግ የቅርብ ጊዜ ክስተቶቹ መሆናቸውን ይናገራሉ። በዚህም በአንድ ጊዜ የተሸለሙትን መለወጥ አለብን ብሎ ማሰብ ትክክል አይደለም። ለውጦች የሚመጡት በጊዜ ሂደት ነው። እናም ተሸላሚዎች ወደ ሥራ የሚገቡበት አጋጣሚ ይፈጠራል።
በዚሁ ተቋም የሽልማትና የገበያ ልማት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መሐመድ እንድሪስ በበኩላቸው፤ እስካሁን አወዳድሮ ከመሸለምና የቴክኒክ ድጋፎችን ከማድረግ ያለፈ ተግባር በተቋሙ አልተሰራም። ምክንያቱ ደግሞ አብዛኛዎቹ የፈጠራ ባለሙያዎች የሚጠይቁት የገንዘብ ድጋፍ በመሆኑ ነው። ይህንን ለማድረግ የሚያስችል መመሪያ አለመዘጋጀቱ እንቅፋት ሆኖባቸዋል።
አቶ ፍቅረ፤ መፍትሄው የቴክኖሎጂ አምራቾች ሳንሆን ተመጋቢ ነንና ይህ ሁኔታ መቀየር፤ እንደ አገር የሚከናወነው የፈጠራ ሥራ በአነስተኛ የፈጠራ ላይ በመሆኑ ማሻሻያዎችን ሰርቶ የፈጠራ ባለቤትነት በማግኘቱ ብቻ መኩራራት እንደማይገባ ያሳስባሉ። መንግሥት የፈጠራ ባለሙያዎችን ለኢኮኖሚው ደጋፊ የሚሆኑበትን ፖሊሲና የህግ ማዕቀፎች ማዘጋጀት እንዳለበት ይመክራሉ። በተቋሙ ኢንዱስትሪንና የፈጠራ ባለሙያን የማገናኘት ሥራ አናሳ ነው። ነገር ግን ባለሙያዎቹንም ሊያበረታታ በሚችል መልኩ በየጊዜው ለሚጠይቁት ነገር የድጋፍ ደብዳቤ ይጻፋል፤ የፍጠራ ባለቤትነት ምርምሮች የገበያ አማራጭ እንዲሆኑ ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ይናገራሉ።
የፈጠራ ውጤታቸው ጥበቃ እንዲያገኝ መደረጉ፤ የፈጠራ ባለሙያዎቹ ባለሀብቶቹን የሚያገኙበት መንገድ እየተመቻቸ መሆኑንና በእጅ ላይ ያሉት ፈጠራዎች ባለሀብቶች እንዲያውቋቸው በአውደ ርዕይ መልኩ መሰራቱ ለችግሮች መፍትሄ እየሰጠ እንደሄደና አሁንም ተጠናክሮ ሊሰራበት ይገባል። እንዲሁም የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችም በሥፋት መተግበር እንዳለባቸው፤ ባለሙያዎቹም የፈጠራ ውጤታቸው ማህበረሰቡን በሚያገለግል ልክ ሊያቀርቡ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።
ዶክተር ሹመቴ በበኩላቸው፤ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መፍትሄ ይሆናሉ ብሎ ባሰባቸው አቅማቸውን አጎልብተው ብድር የሚያገኙበትን ሁኔታ በማመቻቸት በራሳቸው ድርጅት ከፍተው እንዲሰሩ፤ ከሌሎች መሥሪያ ቤቶች ጋር በየሦስት ወሩ በመገናኘት ለፈጠራ ባለሙያዎቹ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ተቋሙ በራሱ የፈጠራ ሥራዎቻቸውን በማልማት ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ይናገራሉ።
ተቋማትና ሽልማት ሰጪው ተናበው መሥራት ካልቻሉ በምንም መልኩ የፈጠራ ባለሙያውም ሆነ አገሪቱ ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደማይችል የሚናገረው ወጣት ዮሐንስ፤ በተለይ ተቋማት ከግል ተጠቃሚነት መውጣት ካልቻሉ ለውጦቹ መቼም ቢሆን የማይታሰቡ ይሆናሉ። የፈጠራ ሥራዎች ለተቋሙ እንደሚጠቅም እየተረዱ እንኳን ያንን ሥራ መደገፍ አለመፈለጋቸው ደግሞ ከግል ተጠቃሚነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ መንግሥት ጉዳዮቹን በሚገባ ሊያያቸው ይገባል ይላል። መንግሥት ሽልማትን ሲያዘጋጅ ትክክለኛ ማዕቀፍ ማበጀት አለበት። ተቋማትም ሥራዎቹን ወደራሳቸው በማምጣት ለሀገር ዕድገት መዋል ይኖርባቸዋል። ሌላ ፕሮጀክት ነድፎ አገሪቱን ለተጨማሪ ወጪ ከመዳረግ እያንዳንዱ የፈጠራ ሥራና የተያዙት ፕሮጀክቶች ተናበው መሰራት ይኖርበታል ባይ ነው።
ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በምርምሩ ዘርፍ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። አሁን ደግሞ በፈጠራ ሥራዎች ላይ የመሸለም ሥራ እየሰራ ነው። ይህ ብቻ በቂ ስላልሆነም የራሱ ዳይሬክቶሬት አዋቅሮ መመሪያዎችን እያዘጋጀ ይገኛል የሚሉት አቶ መሐመድ፤ ከ2004 ጀምሮ 32 የፈጠራ ባለሙያዎችን ለመሸለም የቻለ ሲሆን፤ በሁለት ዙር ስልጠና ሰጥቶ ችግራቸውን እንደለየ ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ ከስድስት ላልበለጡ የፈጠራ ሥራዎች ብቻ ድጋፍ እንደተደረገ ይናገራሉ። ይህ ደግሞ የሆነው ጥያቄው ገንዘብን ማዕከል ያደረገ በመሆኑ ስለነበርና ይህን ለማድረግ መመሪያ ያለመኖሩ ችግር መሆኑን ያስረዳሉ።
ከ1996እስከ 2010ጥር ድረስ በግልጋሎት ሞዴል 2607 አመልካቾች ቀርበው ተቀባይነት ያገኙት 818ብቻ ናቸው። በፈጠራ ባለቤትነት መብት ደግሞ 64ቱ አመልክተው 3ብቻ እውቅና መሰጠታቸውን የሚናገሩት አቶ ፍቅረ፤ የፈጠራ ሥራዎች ውጤታማ የሚሆኑት በመንግሥት እገዛ ነው ተብሎ መታመኑ ተገቢ አይደለም። እነዚህ ችግሮች በዚህ ከቀጠሉ ደግሞ እንደ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ውጤቶች የሸልፍ ማድመቂያ ይሆናሉ፤ የፈጠራ ባለቤትነት እውቅና መስጠትና መሸለምም ይቆማል። ተቋማቱ የያዙትን ግብ እንዲስቱና የተሰጠው ተልዕኮ እንዳይሳካ ያደርጋል ይላሉ።
ወጣት ዮሐንስ፤ የፈጠራ ባለሙያዎች ችግር በርካታ ነው። የገቢ ምንጫቸውን በፈጠራ ሥራቸው ላይ አድርገው እንዳይንቀሳቀሱ ያደርጋል። ይህ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ ማንም የፈጠራ ባለሙያ ለእንጀራ ሳይሆን የፈጠራ ጥማቱን ለማርካት ሲል ብቻ እንዲሰራ ይሆናል። በዚህም አገሪቱ በምትፈልገው ልክ ሳትጠቀም እንዳትቀር፣ ባለሙያውም ድካም ብቻ እንዲተርፈውና አገሪቱ የሌላ አገር የፈጠራ ውጤት ጠባቂ እንድትሆን ያደርጋታል ይላል።
ዶክተር ሹመቴና አቶ መሐመድ በበኩላቸው፤ የሚጠበቀውን ያህል ለውጦች ባለማምጣታቸው ተቋማቱ እንዳይኖሩ ያደርጋል፤ ሰዎችም በሥራቸው እንዳይበረታቱ ይሆናሉ። አገሪቱም ብትሆን ካላት የሰው ኃይል የምትፈልገውን ጥቅም እንዳታገኝ፣ ኢኮኖሚዋ እንዳያድግና ሁሌ የውጭ ቴክኖሎጂዎችን ጠባቂ ሆና እንደምትቀጥል ያስረዳሉ። 

ዜና ትንታኔ
ጽጌረዳ ጫንያለው

 

 

Published in የሀገር ውስጥ
Sunday, 04 March 2018 00:11

ባህል ከተማ ገባ!

ጎበዝ! በከተማ ህዝብ ላይ ፍትሃዊ ያልሆነ ወቀሳ ስናካሂድ ቆይተናል፡፡ የቋንቋ መበላሸት ሲነሳ የከተማው ነዋሪ፣ የባህል መበረዝ ሲነሳ የከተማው ነዋሪ፣ የሱስ ነገር ሲነሳ የከተማው ነዋሪ ነው የሚወቀሰው፤ አልበዛም እንዴ ግን?
ግዴለም ከተሜዎች አይዟችሁ ዛሬ እናንተን ላደንቅ ተነስቻለሁ፡፡ አድናቆቴን ልዩ የሚያደርገው ደግሞ እኔ የገጠር ልጅ ሆኜ እናንተን ሳደንቅ ነው፡፡ በእርግጥ ሰው የራሱን ሳይሆን የሚያደንቀው የሌላውን ነው፡፡ የሆነው ሆኖ ግን ከተሜን በማድነቅ እኔ የመጀመሪያው ነኝ ማለት ነው? ይሄማ እንዴት ይሆናል? ይሄ ሁሉ ከገጠር ወደ ከተማ ያለ ፍልሰት ታዲያ ከተሜን ቢያደንቅ አይደል? ቆይ ግን ገጠርን መተቸትና መውቀስ ወንጀል ነው ያለው ማነው?(ከተሜው ብቻ ምን በወጣው!)
በቃ የኔን አድናቆት በአንድ ነገር ላይ ብቻ ላድርገው፡፡ በዚህ አድናቆቴ ግን የመጀመሪያው ሰው ሳልሆን አልቀርም፡፡ ጸሐፊውም፣ ዘፋኙም፣ ባለሥልጣኑም፤ ስለ አገር ባህል ሲያወራ ምሳሌ የሚጠቅሰው ገጠሩን ነው፡፡ የባህል ምግብ ነገር ሲነሳ ገጠሩን ነው፡፡ የባህል ልብስ ሲነሳ ገጠሩን ነው፡፡ ጎበዝ! ልብ ያላልነው ነገር አለ፡፡
ባህል ከገጠር ጥርግ ብሎ ወደ ከተማ ሊገባ እየተንደረደረ ይመስላል፡፡ በገጠር አካባቢ በጣም ብዙ ነገሮችን እየታዘብኩ ነው፡፡ ዘመናዊ የሆኑ እየመሰላቸው መጣል የሌለበትን ባህል ነው እየጣሉ ያሉት፡፡ በተለይም ይሄ ‹‹ጎጂ ባህል›› የሚል ቃል ፋሽን ሆኗል፡፡ የባህል ተመራማሪዎች ‹‹ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት እንጂ ጎጂ ባህል የሚባል የለም›› ይላሉ፡፡ በገጠር አካባቢ ግን ጎጂ ባህል የሚለው ቃል ተለምዷል፡፡ የባህል ቀሚስ መልበስ ጎጂ ባህል፣ በስፌት ዕቃ መብላት ጎጂ ባህል፣ የሸክላ ዕቃ መጠቀም ጎጂ ባህል፣ ጥጥ መፍተል ጎጂ ባህል… ብቻ ምን ልበላችሁ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ቀልብ የምትስብባቸው የባህል ቁሶች ጎጂ ባህል እየተባሉ ነው፡፡
እነዚህን የገጠር ሰዎች ከመውቀሴ በፊት ግን አንድ የምወቅሰው አካል አለኝ፡፡ በ1990ዎቹ አካባቢ ‹‹የጎጂ ባህል አስወጋጅ ኮሚቴ›› የሚባል ነበር፡፡ ይህ ኮሚቴ በ‹‹ሰዎች ለሰዎች ድርጅት›› ድጋፍ ሲንቀሳቀስ የነበረ ነው፡፡ የሰዎች ለሰዎች ድርጅት በአገራችን በርካታ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን ሰርቷል፤ በማህበራዊና ጤና ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ግንዛቤን የሚለውጡ ሥራዎችን ሰርቷል፡፡ ይሁን እንጂ የጎጂ ባህል አስወጋጅ ኮሚቴው ላይ ያልተጠና ሥራ የተሰራ ይመስለኛል፡፡ ወይም ደግሞ ይሄ ስህተት የተፈጠረው ከየአካባቢው የጎጂ ባህል አስወጋጅ ኮሚቴ አባላት ሊሆን ይችላል፡፡
ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች እየሄዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ይሰጡ ነበር፡፡ ትምህርቱን የሚሰጡት ሰዎች ሥለባህል ያላቸው ግንዛቤ ያን ያህል ነው፡፡ ‹‹በሉ›› የተባሉትን ብቻ የሚሉ ናቸው፡፡ እናም ትምህርቱን ሲሰጡ የአካባቢው ወግና ባህል ሁሉ ጎጂ እንደሆነና መወገድ እንዳለበት ነው፡፡ ሆን ብለው ይህን ባያደርጉ እንኳን ለማህበረሰቡ ያሥረዱበት መንገድ የአካባቢያቸውን ወግና ባህል እንዳይኮሩበት አድርጓል፡፡
ለምሳሌ እኔ ባደኩበት አካባቢ እንኳን የማሥታውሰው የልጅአገረዶች ጨዋታ ነበር፡፡ ይህን የልጅ አገረዶች ጨዋታ ከጎጂ ባህል ጋር ቀላቅለው ነው ያሥተማሯቸው፡፡ ልጅአገረድ የሆነች ሴት የጠፍር መቀነት መታጠቅ ኋላቀር እንደሆነ ነው ያሥተማሯቸው፡፡
ያ የልጅአገረዶች ጨዋታ ግን ጨዋታ እንጂ ምንም ጉዳት ያልነበረው ነው፤ የጠፍር መቀነቱም አንዲት ልጅአገረድ ያላገባች መሆኗ የሚታወቅበት ነው፡፡ እንዲህ አይነት የአጨዋወትና የአለባበስ ባህሎች በየትኛውም አገር ያሉ ናቸው፡፡ ምናልባት የዚያ ተጽዕኖ ሊሆን ይችላል ዛሬ ላይ ይሄ ባህል የለም፡፡ በጣም አልፎ አልፎ የልጅአገረዶች ጨዋታ ቢኖርም የጠፍር መቀነቱ ቀርቷል፡፡ ይሄ ታዲያ ልክ ነው ትላላችሁ?
እንዳልኳችሁ ባህል ወደ ከተማ እየገባ ነው፡፡ የእንቁጣጣሽ፣ የመስቀል፣ የጥምቀት የቡሄ… በዓላት መነሻቸው የገጠሩ ባህል ነበር፡፡ ዛሬ ላይ የቡሄ በዓል ደምቆ የሚታየው አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ የገጠር እረኞች ቡሄን እስከነጭራሹም እየረሱት ነው፡፡ አባቶች ብቻ ወቅቱ የፍልሰታ ጾም ሥለሆነ በጾም ያስታውሱታል፡፡ ልጆች ጎጂ ባህል ነው ብለው ትተውታል፡፡
የጥምቀት በዓል መነሻው የገጠሩ ባህል ነበር፤ ዛሬ ላይ ግን በድምቀት የሚከበረው ጃንሜዳ(አዲስ አበባ) ውስጥ ነው፡፡ እዚህ ላይ ‹‹በሀርሞኒካ የተበረዘ ነው›› በሚለው ወቀሳ አልሥማማም፡፡ እርግጥ ነው በአታሞ ቢሆን ይመረጥ ነበር፤ ግን ይህንኑም ያሰቡት እነርሱ ናቸው፡፡ ገጠር እኮ ጭራሹንም እየቀረ ነው፡፡ አታሞ መሥራትን ጎጂ ባህል ነው ብለውታል፡፡ እንግዲህ አስቡት! ምዕራባውያን ሀርሞኒካን፣ ትራምፔትን፣ ቫዮሊንን ጎጂ ባህል ነው ብለው ቢጥሉት እንደ ማለት እኮ ነው፡፡ ያደርጉታል?
ለቡሄ ሰሞን በየቤቱ ሆያ ሆየ የሚባለው አዲስ አበባ ውሥጥ ነው፡፡ በገጠር አካባቢ ልጆች ቢፈልጉ እንኳን ወላጆቻቸው እየከለከሏቸው ነው፡፡ ‹‹ደግሞ ድሮ የቀረውን›› ነው የሚሏቸው፡፡ የታደሉት እንዲህ አይነት ጨዋታዎችን በፊልም እየሰሩ ይሸጣሉ፤ በዩኔስኮ ያሥመዘግባሉ፤ የኛዎቹ ደግሞ ‹‹ኋላቀርነት›› አሉት፡፡
ቆይ ግን ይሄ የኛ ባህል ኋላቀር የተባለው በምን ቀድመን ሄደን ነው? ችግራችን እኮ ከምዕራባውያን የማንኮርጀው የሚጠቅመውን ሳይሆን የሚጎዳውን መሆኑ ነው፡፡ ራቁት መሄድን ሥንኮርጅ የማንበብ ባህላቸውን ግን አንኮርጅም፡፡ ምንነቱ ያልታወቀን ቀለም ሲቀቡ አይተን ሥንቀባ እንዴት እንደተሰራ ግን አንኮርጅም(እንኳን ሌላ ከላዩ ላይ ያለውን ጽሑፍ አናነብም)፤ የእነርሱን የፍቅረኞች ቀን ሥናከብር የኛ የልጃገረዶች ጨዋታ ግን ኋላቀር ሆነብን፡፡ የእነርሱም እኮ አንድ ‹‹ቫላንታይን›› የተባለ ቄስ የጀመረው ነው፡፡
ከተሜዎች ከምዕራባውያን ሲኮርጁ የገጠሩ አካባቢ ደግሞ ከከተሜው ኮርጆ በልጦ ተገኘ፡፡ የተኮረጀ ነገር ምንነቱ ሥለማይታወቅ የሚጎዳውንም እንወስዳለን፡፡ ለምሳሌ አንድ በራሥ መተማመን የሌለው ተማሪ ሲኮርጅ ትክክለኛ መልስ መሆኑን ሳያውቅ ነው፡፡ የራሱን ትክክለኛ መልሥ ሰርዞ የሌላ ሰው የተሳሳተ መልሥ ሊሞላ ይችላል፡፡
ወቀሳየን ትንሽ ጠንከር ላድርገውና በተለይ ደግሞ ትንንሽ ከተሞች ውሥጥ አጉል አመለካከት ነው ያለው፡፡ ወይ የገጠሩን ባህል አልያዙ ወይ የከተማውን ባህል አልያዙ፤ መሃል ላይ የዋዠቀ ነገር ነው፡፡ ትልልቅ ከተሞች ውሥጥ ብዙ ለባህል ጠንቃቃ ሰዎች ናቸው ያሉት፡፡ ማጨስ፣ መቃም ነውር ነው፡፡ ገና ጀማሪ አራዳ ግን ሳይቅሙና ሳያጨሱ መኖር ነውር ሊመስለው ሁሉ ይችላል፡፡
አሁን አሁን በገጠራማ ከተሞች ውሥጥ በጣም ነውር የሆነ ነገር እየሰማን ነው፡፡ ገና የ10 እና የ12 ዓመት ልጅ ድንግል ሆኖ መቆየት ነውር እየመሰላት ነው፡፡ 18 ዓመት ያልሞላት ልጅ ጽንስ ለማሥወረድ ሥትጥር ሕይወቷንም ሥታጣ እየሰማን ነው፡፡ ትልልቅ ከተማ ውሥጥ ያሉት ግን በራሥ መተማመን ያላቸው ናቸው፡፡
በአለባበስም ቢሆን አሁን አሁን የባህል ልብስ ወደ ከተማ እየገባ ነው፡፡ ይቺኛዋ ነገር እንኳን በጣም አከራካሪ ናት፡፡ ምክንያቱም የባህል ልብስ የለበሱም የምናየው ከተማ ውሥጥ ነው፤ በጣም መረን የለቀቀ ራቁት አለባበስም የምናየው ከተማ ውሥጥ ነው፡፡ እዚህ ላይ ግን ገጠሩን ባመሰግን ሳይሻለኝ አይቀርም፡፡
እንግዲህ ባህልንና ወግን በመጠበቅ ወይ እልም ያለ ገጠር ወይ ደግሞ ቅልጥ ያለ ከተማ ነው የሚሻል ማለት ነው፡፡ ይሄ መሃል ላይ ያለው ለኩረጃ በጣም ተጋላጭ ነው፡፡ እስኪ ነገሩን እንደ ግለሰብ እንኳን ታዘቡት፡፡ ትልቅ ከተማ ውስጥ ተወልዶ፣ እናትና አባቱ በሥነ ሥርዓት ያሳደጉት ልጅ በራሥ መተማመን ያለው፣ መጠጣት፣ ማጨሥ፣ መቃም ነውር መሆኑን የሚያውቅ ነው፡፡ አራዳነት ለእሱ መቃምና ማጨሥ አይደለም፡፡ አንድ እልም ካለ ገጠር ውሥጥ የመጣ ወጣትም እንደዚሁ ነው፡፡
በእነዚህ መካከል ውስጥ ያለውን ብትታዘቡ ግን ይለያል፡፡ ‹‹ሱሪህን ከፍ አድርገህ ታጠቅ›› ብትሉት ‹‹ፋራ ነኝ እንዴ እኔ!›› ሊል ይችላል፡፡ ‹‹መቃምና ማጨስ ጎጂ ነው›› ብትሉት ሊስቅባችሁ ሁሉ ይችላል፡፡ ምክንያቱም በራሥ መተማመን የለውም፡፡ ይህን ካላደረገ አራዳ ሊመሥል አይችልም፡፡
ሰምታችኋል የአራዳ ልጆች? እናንተን ነው ሳደንቅ የቆየሁ፡፡ ይሄ ማለት ግን እነ ቅጠለ በላን አይጨምርም፡፡ እነርሱ ለእኔ ፋራ እንጂ አራዳ አይደሉም፡፡ እኔ ያልኩት በዓላት ሲመጡ በአገር ባህል ደምቀው ጎዳና የሚያጸዱትን፣ እንግዳ የሚቀበሉትን፣ ስለአገራቸው የሚያነቡትን ነው፡፡
ኧረ ሥለነዚህ ሰዎች ሌላም ምሥክርነት ልስጥ፡፡ እስኪ የበዓል ሰሞን ወደ ሾላ ገበያ፣ ሽሮሜዳ፣ አዲሱ ገበያ፣ ቀጨኔ መድኃኒዓለም… አካባቢዎች ሂዱ፡፡ የማታዩት የቅመማቅመም አይነት፣ የጌጣጌጥ አይነት የለም፡፡ ለሽታ ተብለው የሚሸጡ የተክል አይነቶች፣ የቅጠላቅጠልና ሥራሥር አይነቶች የሚሸጡት አዲስ አበባ ነው፡፡ ‹‹ደግሞ ከተማ ማን ሊገዛቸው ነው›› እያልኩ ሥደነቅ ለካ እየተጠቀመበት ያለው ከተሜው ነው፡፡ እንዲህ ነው አራዳነት የምር!

ዋለልኝ አየለ

Published in መዝናኛ
Sunday, 04 March 2018 00:06

በጥበብ «ጉም ጉም»

በልጅነታችን ምን መሆን እንደምንፈልግ ስንጠየቅ የምንመኘውን ወይም በወቅቱ ያለንን ችሎታ መሰረት በማድረግ እንናገራለን። አንዳንዱ ከልጅነቱ ጀምሮ ሲመኘው የነበረውን ይሆናል። ከልጅነቱ ጀምሮ የነበረው ተሰጥዖ ሕይወቱ ይሆናል። አንዳንዱ ደግሞ ጭራሽ ያላሰበውን ሲሆን እንመለከታለን። የዛሬ እንግዳችን በስፖርት ዝነኛ መሆን ነበር ምኞቷ፤ ይሁን እንጅ ህይወት በሌላ መንገድ መራቻትና በሙዚቃው ዓለም ታዋቂ ሆናለች። በሙዚቃ ሕይወቷ ዙሪያ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቆይታ አድርጋለች። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- «አሁን ምን ላወራ ነው?» ብለሽ ሀሳብሽን ለማጋራት ተጨንቀሽ ነበር፤ ለምን ይሆን?
መሰረት፡- ለምን መሰለህ? ለህዝቡ የሆነ ነገር ይዘን መምጣት አለብን። ምንም ነገር ሳንይዝ ሚዲያ ላይ መጥቶ ማውራት እኮ ይከብዳል። እና ለዚያ ብዬ ነው ትንሽ ከበድ ብሎኝ የነበረው።
አዲስ ዘመን፡- እስካሁን የሰራሻቸው ሥራዎች እኮ ብዙ ያስወራሉ፤ አድናቂዎችም «የት ናት?» ማለታቸው አልቀረም። እናም እስካሁን በሰራሻቸው ሥራዎችና አጠቃላይ በሙዚቃ ሕይወትሽ ዙሪያ ትንሽ አጫውችን?
መሰረት፡- እሺ እንግዲህ ካልክ ይሁን(ሳቅ)
አዲስ ዘመን፡- እስኪ ብዙ ካወራን በኋላም ቢሆን ራስሽን አስተዋውቂን?
መሰረት፡- በመጀመሪያ እንግዳ ሥላደረጋችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ። አርቲስት መሰረት በለጠ(ጉምጉም) እባላለሁ፡፡ ተወልጄ ያደኩት ቀደም በነበረው አጠራር መርሐቤቴ አውራጃ በአሁኑ መርሐቤቴ ወረዳ ነው፡፡ ልዩ ቦታው ዓለም ከተማ ይባላል። ቤተሰቦቼ በሥራ አጋጣሚ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ እኔም አብሬ መጣሁ፡፡ እንደመጣሁም ልደታ ባልቻ አባ ነፍሶ ነበር የተማርኩት፡፡ ቤተሰብ እንደገና ወደ ክፍለ ሀገር ሲመለሱም አብሬ ተመለስኩ፡፡ መርሐቤቴ እስከ አሥረኛ ክፍል ተማርኩ፡፡ 11ኛ እና 12ኛ ክፍል ሐረር በመሄድ ትምህርቴን ተከታተልኩ።
አዲስ ዘመን፡- ከልጅነትሽ ጀምሮ ዘፋኝ እንደምትሆኚ ታውቂ ነበር? እንዴት ወደ ሙዚቃው ልትገቢ የቻልሽ?
መሰረት፡- ተማሪ እያለሁ ሐረር ምሥራቅ ዕዝ የሙዚቃ ክፍል ሙዚቀኛ ይቀጥራል ሲባል ሰማሁ። ይህን ስሰማ ከቤተሰብ ጠፍቼ ወደ ሐረር ተጓዝኩ። ሐረር እንደሄድኩም የምሥራቅ ዕዝ ተቀጠርኩ። ወደ ዘፈን የገባሁት በዘፈን ታዋቂ እሆናለሁ በማለት እንጀራዬ ይሄ ነው ብዬ አይደለም። እንዲያውም በልጅነቴ የምታወቀው የአክሮባት ስፖርት በመሥራት ነው። መርሐቤቴ እያለሁ ስፖርት እሰራ ነበርና ዘፈን ከመቻሌ በላይ የምታወቀው ስፖርት መስራት እንደምችል ነበር።
በአንድ የስፖርት ዝግጅት ላይ መርሐቤቴ አውራጃን ወክለን ወደ ዝዋይ ፖሊስ ኪነት ሄደን ነበር፡፡ እዚያ የፖሊስ ኪነት ዝግጅት ላይ እነ ሂሩት በቀለና ሌሎች ታዋቂ ዘፋኞች የስፖርት ዝግጅቱን ለማድመቅ መጥተዋል። ማታ ማታ በሚኖረው ዝግጅት ሂሩት በቀለን ስትዘፍን አያት ነበር። የዚህ ጊዜ ምኞቴ ሁሉ ጥቅልል ብሎ «መቼ ይሆን እኔም እንዲህ የምዘፍነው?» አልኩ። ግጥሟም ዜማውም አልረሳኝ አለ፡፡ ይሄ አጋጣሚ ቀልቤ ወደ ዘፈኑ እንዲሳብ ያደረገበት ወቅት ነበር።
ከፖሊስ ኪነት ወደ መርሐቤቴ እንደተመለስን የታዳጊ ስፖርት፣ የታዳጊ ኪነት፣ የወጣት ስፖርት፣ የወጣት ኪነት የሚባል ስለነበር በእነዚያ ውስጥ መሳተፍ ጀመርኩ፡፡ የታዳጊ ኪነት ውስጥ እያለሁ በአክሮባት፣ በእጅ ኳስ፣ በቅርጫት ኳስ የስፖርት አይነቶች እሳተፍ ነበር፡፡
እዚሁ የታዳጊ ኪነት ውስጥ እያለሁ ነው እንግዲህ ወደ ዘፈኑ እያዘነበልኩ የመጣሁት፡፡ የእነ ሂሩትን፣ የእነ ጥላሁን ገሠሠን ዘፈን የሴት የወንድ ሳልል እዘፍን ነበር፡፡ ስዘፍን የሚሰሙኝ ሁሉ እንደምችል ይነግሩኛል። በ1980 ዓ.ም ነበር ሐረር የምሥራቅ ዕዝ ሙዚቀኞችን ይቀጥራል ሲባል ሰምተን ሦስት ሆነን የሄድነው። በዚያም ፈተና ነበረና በጥሩ አድናቆትና በጥሩ ውጤት አለፍኩ። በወቅቱ የእነ አሰፉ ደባልቄ፣ የሺመቤት ዱባለ፣ የፍቅርአዲስ ነቃጥበብ ዘፈን ተደማጭ ነበር።
ምሥራቅ ዕዝ እያለን ውሃ የምንቀዳው በቦኖ ወረፋ ይዘን ነበር። ወረፋ እስከሚደርስ ድረስ እኔ የሙዚቃ ቤቱ በር ላይ ቆሜ ከዘፋኞቹ ጋር አብሬ እዘፍናለሁ። ልጅነቱም ስለነበር ነው መሰለኝ ሀፍረት እንኳን አልነበረኝም። እንዲህ እንዲህ እያልኩ ወደ ሙዚቃው ሕይወት ገባሁ።
አዲስ ዘመን፡- አባትሽ ቄስ ናቸው፤ ወደ ሙዚቃው ሕይወት ስትገቢ ከቤተሰብ ከባድ ፈተና ነበረብሽ አሉ። እስኪ ምን እንደሚመስል አጫውችን?
መሰረት፡- መጀመሪያ ታዳጊ ኪነት እየሰራሁ ብዙም የጎላ ስላልነበር ተቃውሞ አልደረሰብኝም። ምሥራቅ ዕዝ ተቀጥሬ በትክክል ወደ ሙያው ስገባ ግን ዘፋኝ መሆኔ ታወቀ። የዚያን ጊዜ የአካባቢው ሰው መገረም ጀመረ። እንዴት የቄስ ልጅ አዝማሪ ይሆናል እያሉ ሀሜቱ ተስፋፋ። ከቤት ውስጥ የነበረው ቁጣ ግን በውጭ የተወራውን ያህል አይደለም። አባቷ ተቆጥቷታል፣ ቤተሰብ ከልክሏታል እየተባለ ብዙ ተወርቷል። የአባቴ ቁጣ ግን የተባለውን ያህል አይደለም።
‹‹ፈጣሪ እንጀራዋን በዚህ ካደረገው መቼስ ምን ይደረጋል›› ነበር ያለው። ፈጣሪ ይህን ሙያ ስለሰጠኝ እኔም በፀጋ ተቀብዬዋለሁ። ሙዚቃ ራሱን የቻለ ሙያ ነው፤ ተሰጥዖም ነው፤ ሕይወት ነው፡፡ አሁን ጥሩ ኑሮ እየኖርኩበትም እገኛለሁ። አሁን የአባቴ ፍላጎት ፈጣሪን የማመሰግንበት መዝሙር እንዳወጣ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አንችስ መዝሙር ለማውጣት ሀሳቡ አለሽ?
መሰረት፡- እግዚአብሔር ለዚህ ከመረጠኝ ሀሳቡና ፍላጎቱ አለኝ፡፡ ይሁን እንጂ ሀሳቡ በራሴ ቢኖርም አሁን ግን አባቴም በዕድሜ እየገፋ ስለሆነ ፈጣሪን አመስግኜ ማየት ይፈልጋል፤ ስለዚህ የኔ ሀሳብ ብቻ ሳይሆን የአባቴም ግፊት አለበት። ‹‹ፈጣሪ ምንም አላሳጣሽምና አመስግኝው›› ይለኛል። እንግዲህ እግዚአብሔር ለዚህ ክብር ያብቃኝና እውን አደርገዋለሁ ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ተማሪ እያለሽ በደብተርሽ ጀርባ ላይ የዘፈን ግጥም ትጽፊያለሽ ይባላል፤ ምን ያህል እውነት ነው?
መሰረት፡- እውነት ነው(ሳቅ) ታዳጊ ኪነት በምሰራበት ጊዜ እርስበርሳችን ፉክክር እናደርግ ነበር፡፡ ጎበዝ ለመባልም ስለምፈልግ ግጥሞችን መያዝ አዘወትራለሁ። ስለዚህ የምዘፍናቸውን ዘፈኖች ግጥም በደብተሬ ላይ እጽፍ ነበር፡፡ በትምህርቴ ግን ሰነፍ አልነበርኩም፤ ጎበዝ ተማሪ ነኝ። ግጥሞችን በደብተሬ ጀርባ ላይ ሳይሆን ቤተሰቦቼ እንዳያዩት መሃል ላይ ነበር የምጽፋቸው፤ ወይም ደግሞ በሉክ ጽፌ ደብተሬ መሃል ውስጥ አስቀምጠዋለሁ።
በዚያን ወቅት መብራት እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዓት ድረስ ብቻ ነበር፡፡ ከስድስት ሰዓት በኋላ በኩራዝ ነው የምናጠናው፡፡ እዚህ ላይ አንድ የማስታውሰው ነገር አለ። ይኸውም አጠናለሁ ብዬ ስዘፍን የተያዝኩት ነው። ላጠና ተቀምጬ በውስጤ ዘፈን ሳንጎራጉር በስሜት ድንገት ድምጼ ወጥቶ ኖሮ ቤት ውስጥ ሰሙኝ፡፡ ‹‹ለካ ትምህርቱን ትተሽ ዘፈን ነው የምታጠኝው›› ብለው ተቆጡኝ።
በወቅቱ ግጥሞቹን በደብተሬ የምጽፈው ካሴት አወጣለሁ ብዬ አልነበረም፡፡ እዚያው ታዳጊ ኪነት ውስጥ በልጦ ለመገኘት ነበር፡፡ ታዳጊ ኪነት ውስጥ በምሰራቸው ሥራዎች ጎበዝ ለመባል እያልኩ ስሰራ ይበልጥ ተሳብኩና ወደ ሙዚቃ ሙያ ውስጥ ገባሁ። ምሥራቅ ዕዝ ሥሰራ ቆየሁ፡፡ እንኳን ህዝቡ እኔም በይፋ ዘፋኝ መሆኔን ያወቅኩት ‹‹ጉም ጉም›› ከወጣ በኋላ ነው፡፡ ካሴቱ ወጣ፤ ህዝቡም በጣም ወደደልኝ።
አዲስ ዘመን፡- እንዲህ ለዘፈን ቅርብ እንድትሆኚ ያደረገሽ ምንድነው? እስኪ የልጅነት ህይወትሽን ንገሪን?
መሰረት፡- እናታችን የቤት እመቤት ናት፤ አባታችን መሃንዲስ ነበር፡፡ መሃንዲስ በያኔው አናጢ ማለት ነው። የግለሰብ መኖሪያ ቤቶችን ሳይጨምር ቤተ ክርስቲያን እንኳን ከሰማንያ በላይ እንደሰራ ይነግረን ነበር፡፡ እናታችን የቤት እመቤት አባታችን የምህንድስና ባለሙያዎች በመሆናቸው በጨዋ አስተዳደግ አሳድገውናል።
ከጓደኞቼ ጋር አገዳ፣ ኩበትና ጭራሮ እየለቀ ምኩ ልጅነቴን አሳልፌያለሁ። የኩበትና ጭራሮ ለቀማውን እንደ ጨዋታ ጭምር ነበር የማየው። አንድ ጊዜ የአክስቴ ሰርግ ነበር። አክስቴ በተክሊል ልታገባ ሰው ሰርግ ላይ ሲጣደፍ እኔ ኩበት ለቀማ ካልሄድኩ ብዬ የሳቁብኝን አልረሳውም። አያታችን (የእናታችን እናት) ከከተማው ውጭ ስለነበር የምትኖረው ሁልጊዜ አርብ አርብ ወደ እሷ ቤት እንሄዳለን። ቤት ውስጥ ሬዲዮ ነበር፡፡ ሁሌም ቅዳሜና እሁድ ሬዲዮ እከታተላለሁ። የኢትዮጵያ ሬዲዮ ላይ እሁድ እሁድ የነበረውን የዘፈን ምርጫ ፕሮግራም አጥብቄ እወደውና እከታተለው ነበር። እዚያ ላይ የዘፋኞችን ስም፣ ግጥሙን፣ ዜማውን ሁሉ ሳይቀረኝ እከታተለዋለሁ፡፡ የምሰማቸውን ዘፈኖች ውሃ ስንቀዳም ሆነ ኩበት ስንለቅም አንጎራጉራቸዋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ከህዝብ ጋር ያስተዋወቀሽ የመጀመሪያ ዘፈንሽ ጉም ጉም ነው፤ ጉም ጉም በወጣበት ጊዜ የአንች ስሜት ምን ነበር? በቃ ዘፋኝ ሆንኩ አልሽ ወይስ...?
መሰረት፡- ጉም ጉምን ስሰራ ከዘፋኞች ለመወዳደርና እኔ በልጬ ለመገኘት አይደለም፡፡ የዘፈን ስሜቱ፣ በሙያው ውስጥ ማለፉ ምን እንደሚመስል ለማየት ነው፤ የኔ ትልቁ ምኞትም ይህ ነበር። ጉም ጉም እንደተሰራ ግን በህዝቡ ዘንድ ተወዳጅ ሆነልኝ። ጉም ጉምን በቀጥታ(ላይቭ) ቴሌቪዥን ላይ ሰራሁት፡፡ እንዴት እንደሰራሁት እንኳን ልብ አልለውም። ዘፈኑ በቴሌቪዥን ሲለቀቅ የአድማጮች አስተያየት ያልጠበቅኩት ሆነ፡፡ እኔ ራሴ እንደገና አዳመጥኩት፡፡ «እንደዚህ አይነት ድምጽ ያላት ልጅ ነበረች እንዴ?» እያሉ ብዙ ሰዎች ተገረሙ፡፡ ትልልቅ ሰዎች ሁሉ ስልኬን እያፈላለጉ ደውለው ይነግሩኝ ነበር፡፡ ሙዚቃ ቤቶች ወዲያውኑ ማነጋገር ጀመሩ። በጉም ጉም ያወቁኝ ሙዚቃ ቤቶች አፈላልገው አገኙኝ፤ ጉም ጉምን ጨምሬ ሙሉ አልበም ሰራሁ።
አዲስ ዘመን፡- ከጉም ጉም በኋላ ‹‹እኔ ሴቷ ልጨው›› የሚል ሙሉ አልበም አውጥተሻል፡፡ ይህኛው አልበምሽ ደግሞ ሙዚቃው ውስጥ ከቆየሽ በኋላ የወጣ ነው፡፡ እስኪ በንጽጽር የትኛው አድካሚ ነበረ? በህዝቡ ውስጥ ተወዳጅ ሆኖልኛል የምትይውስ የትኛውን ነው?
መሰረት፡- በሁሉም ሥራዎቼ ውስጥ ጉም ጉም አለ። በሌሎች ዘፈኖቼ ውስጥ ግጥም ዜማ እየተቀያየረ ቢመጣም መነሻዬ ጉም ጉም ነው። ከዚያ ወዲህ ባወጣኋቸው አልበሞች እንኳን «መሰረት ጉም ጉም» እየተባልኩ ነው የምጠራው። በጉም ጉም አልበም ውስጥ ያሉት እነ «ሰው አየሁ» ዘፈኖች መነሻዬ ናቸው። በሁሉም ሥራዎቼ ውስጥ ደክሜያለሁ። ይሄ ከዚህ ይበልጣል የምለው አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ብዙ የባህል ዘፋኞች ውጭ አገር ይኖራሉ፤ አንቺ ደግሞ ውጭ አገር መኖር አትፈልጊም አሉ፤ ለምንድነው?
መሰረት፡-እኔ ውጭ አገር መኖር አልፈልግም፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋና ምክንያቴ አገሬ ውስጥ ያለኝ ደንበኛ እንዳያጣኝ ነው። አሁን ያለሁበት ቦታ ላይ ያደረሰኝ የአገሬ ህዝብ አድናቆት ነው፤ የአገሬ የሙዚቃ ባለሙያ ነው፤ የአገሬ ደንበኞች ናቸው። እነዚህን ሁሉ ትቼ ውጭ አገር መኖር አልፈልግም። እኔ እንደማንኛውም አርቲስት ውጭ አገር ኮንሰርት ማዘጋጀት እችል ነበር። በውጭ አገር በጣም ብዙ አድናቂዎች አሉኝ።
ኑሮዬንም በውጭ ማድረግ እችላለሁ። ግን ለዚህ ያበቃኝን ደንበኛ ትቼ የምሄደው ለምንድው? እኔን የሚፈልግ ሰው ደውሎ ‹‹የለችም›› እንዲባል አልፈልግም። አሁን ብተወውም ቀደም ሲል የምሽት ክለብ እሰራ ነበር። በክለቡ ውስጥ ብዙ አድናቂ ይመጣል። ያ ሁሉ አድናቂ እኔን ብሎ በቦታው ስለሚገኝ የክለቡ ባለቤት እኔን ፈልጎ ያሰራኛል፤ ስለዚህም ይህ ደንበኛዬ ሊያጣኝ አይገባም። አድናቂዎች ደግሞ ከአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ከክልል ድረስ ይመጣሉ።
በአንድ የምሽት ክበብ ውስጥ ስሰራ ብዙ እቆያለሁ። አሁን እስከተውኩበት ድረስ የሰራሁ ባቸው ክለቦች ከሦስት አይበልጡም። እነዚህ ውስጥ ስሰራ ብዛት ያለው ደንበኛ ይመጣ ነበር፡፡ የምሰራውም ከታላላቆቹ ከነ ተዘራ ኃብተሚካኤል፣ አባባ ተስፋዬና ከማዕከላዊ ዕዝ አርቲስቶች ጋር ነበር። ይሄ ሁሉ ባለበት ውጭ አገር ሄዶ መኖር አልፈልግም።
አዲስ ዘመን፡- ለምን የምሽት ክለብ መስራት አቆምሽ?
መሰረት፡- አሁን እኮ የልጅ አሳዳጊ ነኝ፤ ቤት ውስጥ የሚሰራው ሥራ ይበዛል፤ ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት መላክ፣ በአጠቃላይ ልጆችን የማሳደግሥራና ቤትን ከመምራት ጋር አይመችም። እስካሁን በሰራሁት ግን ውጤታማ ነኝ ብዬ አምናለሁ። ብዙ ልምድ አግኝቸበታለሁ። ለምሳሌ በክራር፣ በከበሮና በማሲንቆ መጫወት የማልችል ይመስለኝ ነበር። የምሽት ክለብ ውስጥ ስሰራ ግን በእነዚህ መሳሪያዎች ሁሉ እጫወት ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል ዘፈኖቻችሁ በካሴት ነበር ወደ አድማጭ የሚደርሱት፤ አሁን ደግሞ በሲዲና በህገወጥ መንገድ በፍላሽ ሆኗል። በአድናቂዎቻችሁ ዘንድ ለመደመጥ የትኛው ምቹ ይመስልሻል?
መሰረት፡- በካሴት ጊዜ የነበረውንማ ምን ብዬ ልንገርህ? ካሴት በጣም ምቹ ነበር፤ ችሎታህ ይታወቅበታል፤ ሥራህ ይከበርልሃል፡፡ በዚያ ላይ ካሴት ሲሆን አድናቂው እንኳን ስለዚያ ዘፋኝ በሚገባ ያውቃል፡፡ በአልበሙ ውስጥ ያሉ የእያንዳንዱ ዜማ መጠሪያ በቅደም ተከተል ይጻፋል፡፡ ‹‹ሀ›› እና ‹‹ለ›› እየተባለ በካሴቱ ሁለቱም ጎን ያሉ ዜማዎች ይነበባሉ፡፡ አድማጮች የትኛው ዘፈን ከየትኛው ቀጥሎ እንደሚመጣ ይረዱበታል። ካሴቱን አዙረው ቴፕ ውስጥ ሲያስገቡት በየትኛው ዘፈን እንደሚጀምር በሚገባ ይገነዘባሉ።
ካሴት በዘፈኑ ውስጥ ለተሳተፉ ሰዎች ሁሉ እውቅና ይሰጣል። በእያንዳንዱ ዜማ ውስጥ በግጥም ማን እንደተሳተፈ፣ ዜማውን ማን እንዳወጣው ይገልጻል፤ የዘፋኙ ፎቶ በጉልህ ይታያል። የማያነቡ ሰዎች እንኳን የማን ካሴት እንደሆነ ያውቁታል። የሚያነቡ ሰዎችም ስለዘፈኑ ብዙ ነገር የሚያውቁበት ነው። ወደ ክፍለ ሀገር ስሄድ እንኳን እረኞች ሁሉ ዘፈኔን ሁሉ ከነግጥሙ ይዘውት ነው የማገኛቸው። አንዱን ዘፈን ከዘፈንኩላቸው ቀጥሎ ያለውንም እንድዘፍንላቸው ይጠይቁኝ ነበር። ‹‹ሰው አየሁን፣ አያ በለው በለውን›› እያሉ ያስታውሳሉ።
ፍላሽ ከመጣ ወዲህ ብዙ ነገር ተበላሽቷል። የሙዚቃው ባለቤት እንኳን ባለቤትነቱን አያገኝበትም። የአንዱ ዘፈን ላይ ስም እንደገና በመጻፍ(rename) ተደርጎ የሌላ ስም ሊጻፍ ይችላል። ማንም ከኮምፒውተር ወደ ኮምፒውተር ሊያዘዋውረው ይችላል። ማንም ኢንተርኔት ላይ ሊጭነው ይችላል። ሰርቶ መጠቀሙ ቢቀር በትክክል እንኳን አድናቂዎቻችን ዘንድ መድረስ አንችልም። እንዲያውም የአሁኑ ዘፋኝ ይህን ያህል ታዋቂ የሆነው በራሱ ጥረት ጎበዝ በመሆኑ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እስኪ ስለትዳርና የቤተሰብ ሁኔታ እናውራ?
መሰረት፡- ባለትዳር ነኝ። እግዚአብሔር ይመስገን በጣም ጥሩ ሕይወት ነው የምኖረው። የሁለት ሴትና የአንድ ወንድ ልጅ እናት ነኝ፡፡ ልጆቼንም ባለቤቴንም በጣም ነው የምወዳቸው።
አዲስ ዘመን፡- እስኪ ከባለቤትሽ ጋር እንዴት ነው የተዋወቃችሁት?
መሰረት፡- የሰው ልጅ በሆነ አጋጣሚ ይተዋወቃል፤ ግን እንደዚህ ተብሎ ይጠየቃል እንዴ?
አዲስ ዘመን፡- ለምን መሰለሽ? ሰዎች የሚያደንቁትን ሰው ብዙ ነገሩን ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡ ይህን ጽሑፍ የሚያነቡ ሰዎች ከባለቤትሽ ጋር እንዴት እንደተዋወቅሽ ማወቅ ቢፈልጉስ?
መሰረት፡- የተዋወቅነው በሥራ አጋጣሚ ነው፤ የግል ሥራ ነው የሚሰራው።
አዲስ ዘመን፡- መጀመሪያ በስፖርት ጥሩ አቋም እንደነበረሽ አጫውተሽናል፤ የስፖርቱ ነገር የት ደረሰ?
መሰረት፡- ስፖርት ብሰራ አሁን እንዲህ ሆኜ ታየኝ ነበር? (ሳቅ) ሐረር እያለሁ ኦጋዴን አንበሳማ የሚባል ክለብ ስለነበር እዚያ እጫወታለሁ፤ ምሥራቅ ዕዝም እንዲሁ እጫወት ነበር። አክሮባት ስጫወት ስምንትና አሥር ሰው ተደርድሮ እነርሱን ዘልዬ እሄድ ነበር። በእሳት ላይ መገልበጥ፣ በእጅ መሄድ ያኔ ለእኔ በጣም ቀላል ስፖርት ነበር። እግዚአብሔር ሕይወትሽ ይሄ ነው ሲለኝ ከስፖርት ወደሙዚቃ ሙያ ገባሁ። እናም ስፖርቱን ከተውኩት ቆይቻለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ በምን እንጠብቅሽ?
መሰረት፡- ከዚህ ቀደም ከጥበቡ ወርቅዬ ጋር የሰራሁት የሰርግ ዘፈን አለ። እሱን ጨምሬ በፊት የሰራኋቸውን ሥራዎቼን በክሊፕ እየሰራሁ እገኛለሁ። አሁን በቪሲዲ የሰራኋቸው አሉ። ዜማዎችን አሰባስቤ ጨርሻለሁ፤ ሁሉንም ከሰራሁ በኋላ በክሊፕ አድናቂዎቼ ጋር ለመድረስ ዝግጅት ላይ ነኝ። አሁን ግን አስቸጋሪ የሆነው በራሳችን ማሳተማችን ነው። በሙዚቃ ቤት ነው ወይስ በምንድነው የምናሳትመው? የሚለው ነው ጥያቄ የሆነብን። ያላቸውን ንብረት ሁሉ ሸጠው በግላቸው ያሳተሙ ምንም ሳያገኙ ዜሮ ሆነው የቀሩ አሉ። ይሄ ሁሉ ችግር ባለበት እርግጠኛ መሆን ባይቻልም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሰርቼ ጨርሻለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በጣም እናመሰግናለን።
መሰረት፡- እኔም እንግዳ ስላደረጋችሁኝ በጣም አመሰግናለሁ።

ዋለልኝ አየለ

Published in ማህበራዊ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።