Items filtered by date: Monday, 05 March 2018

ሃገራችን ከድህነት ለመውጣት ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን እያደረገች ትገኛለች፡፡ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ እቅድ ተይዘው ተግባራዊ እየተደረጉ የሚገኙ እቅዶችም ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ ከነዚህም ውስጥ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ የተካተቱ ፕሮጀክቶችና ሌሎች የመሰረተ ልማትና የኢንዱስትሪ ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህን ስራዎች ለማገዝ ደግሞ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል፡፡
የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ በተለይ ወጣቶችን የሙያ ባለቤት ለማድረግ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ወጣቶችን በማሰልጠንና ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግ ብቃት ያለው የሰው ሃይል ከሚያቀርቡ ተቋማት አንዱ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ከነዚህ ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ሰልጣኞች ለትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆኑ ጥሬ እቃዎችን በማቅረብ ኢንዱስትሪው እርስ በርሱ እንዲደጋገፉ የራሳቸውን አስተዋፅኦ ያበረክታሉ፡፡
በተለይ ሃገራችን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የእድገትና ትራንስፎርሜሽ እቅድ ነድፋ ተግባራዊ እያደረገች ባለችበት በአሁኑ ወቅት እነዚህ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚኖራቸው ድርሻ የላቀ ነው፡፡
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአብዛኛው በግብርና ላይ የተመሰረተ ከመሆኑም ባሻገር ግብርናውም ቢሆን በኋላቀር የአስተራረስ ዘዴ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር ከፍተኛ ጥረትና ትጋትን ይጠይቃል፡፡
የሃገራችንን ነባራዊ ሀኔታ ስንመለከት ደግሞ በአንድ በኩል በከተማ ያለውን የስራ አጥነት ችግር ለመፍታት በርካታ የሰው ጉልበት የሚጠቀሙ ትናንሽ ኢንዱስትሪዎችን ማሳደግ ተገቢ መሆኑን ያመላክታሉ፡፡ ምክንያቱም ሃገራችን ያላት የካፒታል አቅም አነስተኛ በመሆኑና በአንጻሩ ያለው የሰው ጉልበት ከፍተኛ በመሆኑ ከዚህ አንጻር የሰው ጉልበትን በሰፊው የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች ጠቀሜታቸው የጎላ ነው፡፡
ለዚህ ደግሞ በተለይ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ወጣቶችን የተለያዩ ሙያዎች ባለቤት በማድረግ በአንድ በኩል በትንሽ ካፒታል ስራ ፈጥረው እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችላቸው ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በአንድ ጊዜ በርካታ ወጣቶችን ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግ ሰፊ የስራ እድሎች እንዲፈጠሩ ያደርጋሉ፡፡
በሌላ በኩል ሃገራችን ለጀመረችው የኢንዱስትሪ መር የኢኮኖሚ ሽግግር ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ሜጋ ፕሮጀክቶች በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ከተሞቻችንም በተለይ አዲስ አበባ በአዲስ መልኩ ፈርሳ እየተገነባች እስክትመስል ድረስ በርካታ የመሰረተ ልማት ስራዎች እየተከናወኑባቸው ይገኛል፡፡ በሃገር ውስጥና በውጭ ባለሃብቶች የሚከፈቱ ኢንዱስትሪዎችም ከዚሁ ጎን ለጎን በስፋት እየተከናወኑ ናቸው፡፡
የቴክኒክና ሙያ ተቋማትም በነዚህ የልማት ስራዎች ዋነኛ ግብዓት በመሆን የሚያገለግሉ በመሆኑ ጠቀሜታቸው የጎላ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በራሳቸውም በሂደት እንዲያድጉና ለሃገር ግንባታም የራሳቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ያስችላቸዋል፡፡
የቴክኒክና ሙያ የስልጠና ዘርፎች ጠቀሜታቸው ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ በተለይ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ እነዚህ ማዕከላት የሚያመርቷቸው የስራ ውጤቶች ከሃገር ውስጥ አልፎ ለውጭ ገበያም መቅረብ የሚያስችል አቅም እየተፈጠረባቸው ይገኛል፡፡
በርግጥ ዘርፎቹ ቀደም ሲል የተለያዩ የአመለካከት ችግሮች የሚስተዋልባቸው ስለነበሩ ውጤታማነታቸው አነስተኛ ነበር፡፡ በተለይ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ላይ የሚሰማሩ ወጣቶች በትምህርት ዘርፉ የወደቁ ተማሪዎች የሚገቡበት ተደርጎ ይወሰድ ስለነበር በህብረተሰቡም ሆነ በራሳቸው በተማሪዎችና በሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም አነስተኛ ግምት ይሰጥ ነበር፡፡
በሌላ በኩል በኢንዱስሪዎችም ቢሆን የነበረው አመለካከት አሁን አሁን እየተቀየረ ቢመጣም የተዛነፈ ነበር፡፡ በተለይ እነዚህን የቴክኒክና ሙያ ምርቶች ለመቀበል የነበረው አመለካከት አነስተኛ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ለዚህም በነዚህ ተቋማት የሚመረቱ የኢንዱስትሪ ውጤቶች ጥራት ያንሳቸዋል ከሚል አመለካከት የመነጨ ነበር፡፡
ያም ሆኖ ግን አሁን አሁን ይህ አመለካከት እየተሰበረ ይገኛል፡፡ በተለይ በነዚህ ተቋማት የሚመረቱ የተለያዩ የኢንዱትሪ መለዋወጫዎች፣ የእደጥበብ ውጤቶች፣ አልባሳት፣ ምግብና መጠጥ ወዘተ በጥራትም ሆነ በማንኛውም መስፈርት ከሌሎች ምርቶች የማያንስበት ሁኔታ እየተፈጠረ መምጣትና ተወዳዳሪነታቸው እያደገ መሄድ ተቀባይነታቸውን እንዲጨምር በማድረግ የአመለካከት ለውጡ እንዲመጣ አድርጓል፡፡
ከዚህም በመነሳት በአሁኑ ጊዜ ከቴከኒክና ሙያ ተመርቀው የሚወጡ ሰልጣኞች በአንድ በኩል ለኢንዱስትሪው ግብዓት የሚሆኑ በርካታ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በማቅረብ የውጭ ምንዛሬን እስከማስቀረት የደረሱ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዶቹ በራሳቸው ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪን ማስቀረት ችለዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በሃገሪቷ ያለውን የስራ አጥነት ችግር ከመፍታት አንጻር ከእነዚህ ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ሰልጣኞች በአንድ በኩል በራሳቸው ስራዎችን በመፍጠርና ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የስራ እድሎችን በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዶቹም በተለያዩ ትላልቅ ተቋማት በመቀጠር ጭምር በኢንዱስትሪ ሽግግሩ ውስጥ የራሳቸውን ድርሻ እየተወጡ ይገኛሉ፡፡
በቀጣይ ዘርፉ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ በዘርፉ ያሉ መልካም ጅማሮዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል እና ተቋማቱንም በሰው ሀይል፣ በአመለካከት፣ በአደረጃጀትና በአሰራር የሚጠናከሩበትን ሁኔታ መፍጠር ተገቢ ነው፡፡
ከዚህም ጎን ለጎን ኢንዱስትሪውን ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር በማስተሳሰር የሚሰጡ ስልጠናዎች ጥራት የሚያድጉበትንና ከተቋማቱ ተመርቀው የሚወጡ ሰልጣኞችም በሚሰሯቸው ስራዎች ጥራት ግንባር ቀደም ሆነው የሚወጡበትን ሁኔታ መፍጠር ተገቢ ነው፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የአመራር ለውጥ ማድረጉን ተከትሎ፤ ቋሚ ብሄራዊ ቡድን መመስረቱ የሚታወስ ነው። ፌዴሬሽኑ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ መሰረትም በድጋሚ ብሄራዊ ቡድኑን ማፍረሱን አስታውቋል። በዓለም አቀፍ ውድድሮች ብሄራዊ ቡድኑን የሚወክሉት አትሌቶችም የተቀመጠውን መስፈርት ሲያሟሉ የሚመረጡ ሲሆን፤ ብሄራዊ ቡድኑን የሚመሩት አሰልጣኞችም ባስመረጧቸው አትሌቶች ቁጥር የሚወሰን ይሆናል። ይህም ማለት አንድ ክለብ በርካታ አትሌቶችን ለብሄራዊ ቡድን የሚያስመርጥ ከሆነ የክለቡ አሰልጣኝ ቡድኑን በዓለም አቀፉ ውድድር ላይም የሚመራ ይሆናል። አሰራሩ በክለቦች ተቀባይነት ያግኝ እንጂ፤ በአንዳንድ ባለሙያዎች ዘንድ ቅሬታ እንዲሁም የአስፈላጊነትና ውጤታማነት ጥያቄ በማስተናገድ ላይ ይገኛል።
ስመጥር አትሌቶችን በማፍራት ስማቸውን ከአትሌቲክሱ እኩል ያስጠሩትና ብሄራዊ ቡድንን በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የመሩት አንጋፋው አሰልጣኝ ቶሎሳ ቆቱ፤ ፌዴሬሽኑ በጀመረው አዲስ አካሄድ አይስማሙም። የስፖርቱ ዋና ዓላማ በዓለም አቀፍ ሻምፒዮናዎች ላይ መሳተፍ ነው፤ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ ደግሞ በክለብ ሳይሆን በብሄራዊ ቡድን መሰራት ይገባዋል የሚል እምነት አላቸው። በተለያዩ ርቀቶች የታወቁ ታላላቅ አትሌቶች ላይ መሰራት የሚገባው ውድድር ሲደርስ ብቻ ሳይሆን ዓመታትን ቀደም ብሎ ነው። ለዚህ ደግሞ አትሌቶቹ መስራት የሚገባቸው አቅም ካላቸው እና አትሌቱን በደንብ ከሚያውቁት አሰልጣኞች ጋር መሆን እንዳለበት ይጠቁማሉ።
አትሌቶች በክለቦቻቸው ውስጥ ሰልጥነው ትልቅ ደረጃ ላይ ከደረሱ ተመጣጣኝ የሆነ ስልጠና ማግኘት አለባቸው የሚሉት አሰልጣኙ፤ ብሄራዊ ቡድንን የሚያሰለጥነውና በክለቦች ውስጥ የሚያሰለጥነው አሰልጣኝ በብቃት፣ በልምድ እና በትምህርት ሊመጣጠኑ እንደማይችሉ ነው የሚጠቁሙት።
በርካታ አትሌቶችን ለብሄራዊ ቡድን በማበርከት በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ክለቦች መካከል አንዱ የመከላከያ ስፖርት ክለብ ነው። ፌዴሬሽኑ የጀመረውን አካሄድም እንደሚደግፉት የክለቡ ኃላፊ ኮሎኔል ንጉሴ አየለ ይገልጻሉ። አትሌቶች የስልጠና ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ከክለባቸው አሰልጣኝ ጋር ነው፤ ለብሄራዊ ቡድን በርካታ አትሌቶችን እያስመረጠም ግን አሰልጣኞችን የሚያስመርጠው አልፎ አልፎ ነው። ይህ ደግሞ አሰልጣኞችን ከማነሳሳት፣ ከሞራል እና ከፍትሃዊነት አንጻር በየጊዜው በክለቦች የሚነሳ ጥያቄ ነበር። ዓላማው አገሪቷን መጥቀም እስከሆነ ድረስም በተግባር ውጤታማ የሆነ አሰልጣኝ እንዲሁም የትኞቹን አትሌቶች አፈራ የሚለው መሆን እንዳለበት ያብራራሉ።
አትሌቶች ለወራትና ለተወሰነ ጊዜ በብሄራዊ ቡድን ተይዘው ስለሰለጠኑ ብቻ ውጤታማ ይሆናሉ ብለው እንደማያስቡ ኃላፊው ይገልጻሉ። ለአትሌቱ ውጤታማነት ወሳኝ የሚሆነው ቀድሞ ያለፈበት የስልጠና ሂደት ነው፤ ለዚህ ደግሞ ተጠቃሽ የሚሆኑት ክለቦች ናቸው። አትሌቶቹ በብሄራዊ ቡድን ሲታቀፉ የተለየ ዓለም አቀፍ ስልጠና ሲያገኙ፣ የቡድን መንፈስ ሲፈጠርባቸው አዳዲስ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን ይላመዳሉ፤ መሰረታዊው ጉዳይ ግን ውጤታማነቱ ነው። የክለብ አሰልጣኞች ልምድ ባይኖራቸውም በአንጋፋ አሰልጣኞች እየተደገፉ ብቁ ወደመሆንና ወደ ውጤታማነት ሊያመሩ እንደሚችሉ ነው የሚጠቁሙት።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም፤ ከዚህ ቀደም አሰልጣኞች ልምዳቸውና ሰርተፊኬታቸው ብቻ እየታየ ለብሄራዊ ቡድን እንደሚመረጡ ይጠቅሳል። አንድ ክለብ በርካታ አሰልጣኞችን ይዞ ከፍተኛ ገንዘብ እያፈሰሰ አትሌቶችን ሲያዘጋጅ ይቆያል፤ ነገር ግን በሌላ የተሻለ ሰርተፍኬት ባለው አሰልጣኝ ክለብ ያዘጋጃቸው አትሌቶች ይመራሉ። ይህ ደግሞ የብዙ ክለቦችና አትሌቶች ምርጫ አለመሆኑን ፌዴሬሽኑ በመገንዘቡ ወደዚህ አሰራር እንደገባ ይገልጻል።
ብሄራዊ ቡድን ላይ ብቻ ተወስነው ክለቦቻ ቸውን የሚያፈርሱ በርካታ አሰልጣኞች መኖራቸውንም ምክትል ፕሬዚዳንቱ ይጠቁማል። አንድ ታዋቂ አትሌት ብቻ ይዘው «እኔ ነኝ ያሰለጠንኩት» በሚል ሽፋን ብሄራዊ ቡድን ላይ የተለጠፉ ብዙዎች ናቸው። በመሆኑም ይህንን ለማስቀረት አዲሱ መንገድ ተመራጭ ከመሆኑም በላይ ክለቦችን በመያዝ ጠንካራ አትሌቶችን ለማፍራት መጣር እንደሚገባቸው የሚያሳይ መሆኑንም ያስረዳል።
ከዚህ ባሻገር አሰራሩ የአትሌቶችን ተገቢነት ሊያስነሳ እንደሚችል ይታሰባል። አትሌቶችን ከመመልመል ጀምሮ ውጤታማ እስኪሆኑ ድረስ የአሰልጣኝ ጥረት ዋናውን ድርሻ ይይዛል። አትሌቶቹ የተሻለ ገቢ ለማግኘት ክለቦች ውስጥ ይቀጠራሉ። ይህ ደግሞ አትሌቱ ለብሄራዊ ቡድን ሲመረጥም ከብቃታቸው ያደረሷቸው አሰልጣኞች ሳይሆኑ በክለብና ክልል አሰልጣኞች መመራታቸው ቅሬታ ሊፈጥር አይችልም? የሚል ጥያቄን ያስነሳል፡፡
ኮሎኔል ንጉሴ፣ አትሌቱ በየትኛውም አሰልጣኝ ሰልጥኖ ሙሉ ብቃት ላይ ቢደርስ የሚጠራው ግን በአገር ዓቀፍ ውድድሮች ላይ በወከለው ክለብ መሆን እንደሚገባው ነው የሚጠቁሙት። አትሌቱ ከየትም ይምጣ ከየት አንድን ክለብ ብቻም ሳይሆን ክልሉንም ሊወክል ስለሚችል፤ ባወዳደረው አካል አሰልጣኝ ሊጠራ ይገባል ባይ ናቸው።
አትሌቶች የብዙ አሰልጣኞች አሻራ ውጤት መሆናቸውን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገብረእግዚአብሄር ያመላክታል። አትሌቶች ከአንዱ ክለብ ወደሌላኛው ክለብ ሲሄዱ አዲስ አሰልጣኝ እንደሚያገኙ እርግጥ ነው። ለብሄራዊ ቡድን ሲመረጡም «እኔ ነኝ ያሰለጠንኩት» ብሎ የሚመጣ ካለ፤ ፌዴሬሽኑ ከመች ጀምሮ አሰለጠነው የሚለውን በቅድሚያ የማጣራት ሥራ ያከናውናል። አሰልጣኙና አትሌቱም በዚህ ላይ የሚስማሙ ከሆነ ብቻ ፌዴሬሽኑ ይቀበለዋል። ነገር ግን የተገቢነት ጥያቄ ሲነሳ ፌዴሬሽኑ የአትሌቱን የኋላ ታሪክ የሚያጣራ ከሆነ፤ የአንድ አትሌትና አሰልጣኝ አብሮነት እስከ ምን ያህል ጊዜ መሆን ይኖርበታል የሚለው መታወቅ አለበት። ፌዴሬሽኑ እስካሁን የወሰነው ነገር ባይኖርም፤ አትሌቱ ለሚሳተፍበት ውድድር «ያዘጋጀው ማነው?» የሚለው ታይቶ አሰልጣኙ ይመረጣል።
አሰራሩ፤ ትናንት በተጠናቀቀው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና አገሪቷን ከወከለው ብሄራዊ ቡድን ጀምሯል። ይሁን እንጂ አሁንም የውጤታማነት ጥያቄ የሚያነሱ ባለሙያዎች በርካታ ናቸው። አንጋፋው አሰልጣኝ ቶሎሳ ቆቱ፤ ፌዴሬሽኑ የጀመረው መንገድ አገሪቷን ውጤታማ አያደርጋትም የሚል እምነት አላቸው። ሃሳባቸውን ሲያብራሩም፤ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በትልልቅ የውድድር መድረኮች ውጤታማ ልትሆን የቻለችው በብሄራዊ ቡድን በመስራት ነው። «በዚህ መንገድ የሚፈለገው ውጤት ከተገኘ ደግሞ ብሄራዊ ቡድኑን ማፍረስ ለምን አስፈለገ?» የሚል ጥያቄም ያነሳሉ።
ፌዴሬሽኑ እዚህ ውሳኔ ላይ ሲደርስም ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሙያተኞች አለማማከሩንም ነው የሚጠቁሙት። አትሌቲክስ የቡድን ሥራ እንደመሆኑ በጋራ ተመካክሮ ያልሰሩት ሥራ መጨረሻው መተዛዘብ እንዳይሆን፤ የፌዴሬሽኑ አመራሮች በድጋሚ ሊያስቡበት እንደሚገባ ያሳስባሉ።
በሂደቱ ሙሉ ድጋፍ እንዳላቸው የገለጹት የመከላከያው ኃላፊ፤ አሰራሩ መልካም ነገርን እንደሚያሳይ እምነታቸው ነው። ቅሬታ የሚያነሱ አሰልጣኞችም በብሄራዊ ቡድን ብቻ መወሰን ሳይሆን ክለብ መያዝ እንዳለባቸው ይጠቁማሉ። ልምድ ያላቸው አሰልጣኞች ውጤታማነታቸውን በክለቦች ላይ በማስመስከር ለብሄራዊ ቡድኖች መመረጥ ስለሚችሉ፤ ክለቦችን ለመያዝ መነሳሳት አለባቸው።
አሰራሩ አዲስ እንደመሆኑ መጠን ቅሬታ ቢቀርብበትም ስለውጤታማነቱ ፌዴሬሽኑ ጥርጣሬ እንደሌለው ምክትል ፕሬዚዳንቱ ያረጋግጣል። የፌዴሬሽኑ መርህ «የሰራ ይብላ» የሚል በመሆኑ፤ አሰልጣኞች በብሄራዊ ቡድን ብቻ ሳይወሰኑ ክለቦች ላይም ማሰልጠን እንደሚገባቸውም ነው ያሳሰበው።

ብርሃን ፈይሳ 

Published in ስፖርት
Monday, 05 March 2018 16:55

ቆም ብለን እናስብ!

ኧረ ወገኖቼ ቆም ብለን እናስብ
ብጥብጥ አንፍጠር በሰበባ ሰበብ
መንገዶችን መዝጋት ንብረትን ማውደም
ሰላም አያመጣም መፍትሄም አይሆንም
ሰላም የሚመጣው መፍትሄ የሚገኘው
አገር ሰላም ሲሆን እኛም ስንኖር ነው
ለሰላም ዋጋ እንስጥ ቁጭ ብለን እናውራ
መፍትሄ ለማምጣት በጋራ እንስራ
ሌላ አገር የለንም ያለን አንድ አገር ነው
ቆም ብለን እናስብ ሁሉም በአገር ነው
በቋንቋ፣ በብሄር በዘር ሳንለያይ
ልክ እንደበፊቱ ተዋደን እንኑር
በፍቅር በአንድ ላይ
የአንዲቷ ኢትዮጵያ
የአንድ እናት ልጆች ነን በፍቅር እንኑር
ሰላም በኢትዮጵያችን በምድራችን ይስፈን፡፡
ሱፐር ኢንቴንደንት ደረጀ እሸቱ
በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት አስተዳደር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ

Published in መዝናኛ
Monday, 05 March 2018 16:54

እንቁላል ጣዪው ታዳጊ

አንዳንዴ ተፈጥሮ ልታዳላ ትችላለች፤ ለአንዱ የሰጠችውን ለሌላኛው መንፈጓ የተለመደ ሃቅ ነው። ለአብነት ያህል ጎበዝ እና ሰነፍ፣ ጠንካራ እና ደካማ፣ ደፋርና ፈሪ፣... የተባሉ ፍጥረታት የተለመዱ ናቸው። ነገር ግን አንዳንዴ ከምትነፍገውም ከምትቸረውም ለየት ታደርግና «አይ ፍጥረት» ታሰኛለች። ከዚህ ቀደም ያልተለመዱ ፍጥረታትን አሊያም አፈጣጠርን ተመልክተን ይሆናል፤ ከሰሞኑ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን እየተሰማ ያለው ዜና ግን «አጀብ» ከማሰኘትም በላይ ነው።
ይህ ለሰሚ ግራ የሚያጋባ ጉዳይ የተሰማው ከወደ ኢንዶኔዢያ ሲሆን፤ አክመል የተሰኘው የ14ዓመቱ ታዳጊ እንቁላል እየጣለ መሆኑ ነው። ወጣቱ ላለፉት ሁለት ዓመታት እንቁላል መጣሉን ተከትሎ ቤተሰቦቹ ጎዋ በተባለችው ከተማ በሚገኝ ሆስፒታል ይወስዱታል። በዚህ ግራ የተጋቡት የህክምና ባለሙያዎችም ታዳጊው «ኤክስ-ሬይ» ያስነሱታል፤ ታዳጊውንም ስለጉዳዩ እንዲነግራቸው ያደርጉታል። ነገር ግን ከምርመራቸውም በላይ ማየት ማመን ነውና በሆስፒታሉ እንዳለ ሁለት እንቁላሎችን ሲጥል ሊመለከቱ ችለዋል።
የአክመል ወላጅ አባት «ልጄ ሆስፒታል እያለ የጣለውን ጨምሮ ላለፉት ሁለት ዓመታት 20 እንቁላሎችን ጥሏል። እንቁላሎቹን ሰብሬ ለመመልከት እንደቻልኩትም ከሆነ በውስጡ ቢጫ የሌለው(አስኳል) ነጭ ፈሳሽ ብቻ የያዘ ነው» ብለዋል። የህክምናው ዓለምም ሆነ ሳይንስ ግን የሰው የውስጥ አካል እንቁላል ሊያመርት የሚችልበት ተፈጥሮ እንደሌለው ነው የሚያመለ ክተው። ታዳጊውን የተመለከቱት ዶክተሮችም «በቀጥታ እንዲህ ነው ብሎ መናገር ባይቻልም፤ ምናልባትም እንቁላሎቹ ወደ ታዳጊው አንጀት በግድ እንዲገቡ የተደረጉ ሊሆን ይችላል» የሚል መላምት ሰጥተዋል።
ነገሩን ይበልጥ ግራ አጋቢ ያደረገው ደግሞ ከሰው ልጅ እንቁላል መመረቱ ብቻም ሳይሆን፤ የምግብ መፈጨት ሂደት በሚከናወንበት አንጀት ውስጥ መሆኑን የሆስፒታሉ ቃል አቀባይ ሙሃመድ ጣዝሊም ለመገናኛ ብዙሃኑ ገልጸዋል። እንደ ደይሊ ኤክስፕረስ ዘገባ ከሆነ ጉዳዩ የመጀመሪያ ሳይሆን፤ ከዚህ ቀደም ካኬክ ሲኒን የተባለ የጃካርታ ነዋሪም ይኸው ችግር ተከስቶበት ነበር። ነገር ግን በእንስሳት የጤና ባለሙያዎች በተደረገው ምርመራ እንቁላሎቹ የሁለት ሳምንት ዕድሜ ያላቸው የዶሮ እንቁላሎች መሆናቸው ተረጋግጧል።

ብርሃን ፈይሳ

Published in መዝናኛ
Monday, 05 March 2018 16:52

“የፈላስፋው ውሃ”

አንድ ንጉስ እጅግ አጥብቆ የሚወደው ፈላስፋ ነበረው፡፡ አብሮት የሚጋበዝ የሆነውን፣ የሚሆነውንም ሁሉ የሚያማክረው፡፡ በዚህ ሁኔታ በጤናና በስምምነት አያሌ ወራት አብረው ሲኖሩ አንድ ቀን ከገበታ ላይ ለምግብ ተቀምጠው ሳሉ ፈላስፋው ድንገት ተነስቶ “አዬዬዬ…..ዬ” አለና እጅግ ተከዘ፡፡ ወደ ምግቡም እምብዛም ነፍሱ አልፈቀደ፡፡ በዚያን ጊዜ ንጉሱ ደንግጦ ያመመው መስሎት “ምነው በደህናህ ነውን” ብሎ ጠየቀው፡፡
ፈላስፋውም እየመላለሰ “አዬ” ማለት ያዘ፡፡
ንጉሱም “ደሞ አመመህን?” ቢለው እንኳን “አላመመኝም” ብሎ መለሰለት፡፡
ንጉሱም “እንግዲያውስ አሁንም አሁንም እየተከዝክ ʻአዬʼ የምትለው ምን ብትሆን ነው?” ብሎ መረመረው፡፡ ፈላስፋው ግን አሁንም ዝም ብሎ “አዬ” ማለቱን ቀጠለ፡፡
ንጉሱም ገሚሱን በቁጣ ገሚሱን በጭንቀት ሆኖ፣ “እንዲህ ያለ ነገር ምንድን ነው? ኧሯ! እባክህን ንገረኝ ምንድን ነው ብልሃቱ?” ብሎ ቢለው
“ክፉ ዘመን የሚመጣብን ቢሆን ነው፤ እንዲህ የምሆነውና የማዝነው” ብሎ መለሰለት ፈላስፋው፡፡
የባሰውኑ በዚህ ነገር ንጉሱ ተጨነቀ፡፡ንጉሱም ነገሩን በፍጥነት እንዲረዳው ፈለገ፡፡ ፈላስፋው ግን መልሶ “አዬ”ውን ያዘ፡፡ ተዚህ ወዲህ ንጉሱ አጥብቆ ፈራ፡፡ “ኧሯ! እባክህን ውሃ አታድርገኝ ንገረኝ” አለው፡፡
ፈላስፋውም ትክዝ ብሎ፣ “እስከ ሦስት ዓመት እንደለመድነው ጊዜ ሁሉ ነው፡፡ ቀጥሎ ግን የሚዘንበው ዝናብ እስከ ሦስት ዓመት ድረስ ሰውም ሆነ፣ እንስሳም ሆነ ፍጡር የተባለ ሁሉን ይመርዛል፡፡ ውሃን የጠጣ ሁሉ ያብዳል፡፡ ወንዙ፣ ምንጩ ባህሩ ሁሉ ዝናቡ ሲዘንብበት ይመረዛልና፡፡ ስለዚህ ውሃ የጠጣ ሁሉ ያብዳል፡፡ ተዚህ የበለጠ ምን የሚያሳዝንና የሚያስተክዝ ነገር አለ?” በማለት አረዳው፡፡
ንጉሱም እንደፈላስፋው አንገቱን ደፍቶ ተራውን ይተክዝ ጀመረ፡፡ ቀጥሎ ጥቂት ጥቂት ተንፍሶ፣ “ስማ እንደዚህ ያለ የማይቻል መዓት ሲመጣብነ ጊዜ ምን ይበጀናል?” ብሎ አማከረው፡፡
“ለዚህማ መቸስ ምን አቅም አለኝ ያሳየኝ ይህ ነው፡፡ ʻበአዋጅ የደህናውን ዝናብ ውሃ ጉድጓድ እያበጀህ አስቀምጥʼ ተብሎ ማስታወቅ ይሻል ይመስለኛል…ለክፉው ዘመን መውጫ እንዲሆን” ብሎ የቻለውን ምክር መከረ፡፡
አዋጁም ሳይውል ሳያድር ተመታ፡፡ ከህዝቡም የፈራ ጉድጓድ ይምስ ጀመር፡፡ ነገሩን የናቀ ግን፣ “ተወው አመሉ ነው! ሁል ጊዜም አዋጅ ይመታና መች አንድ ነገር ሆኖ ያውቃል? ደግሞ ያሁኑስ የሚያስደንቅ አዋጅ ነው! ተግዜር ጋራ ተማክረዋልን?” እያለ ያፌዝ ጀመር፡፡ ከቤተ መንግስቱ ደግሞ ጉድጓድ ሁሉ ተሰናድቶ ተምሶ የደህናውን ዝናብ ውሃ አከማቹበት፡፡ በቁልፍም ተቆለፈ፡፡ ፈሩትም እንደዚሁ አደረጉ፡፡
ያ ቀን መድረሱ አልቀረምና ደረሰ፡፡ ገና መዝነብ ሲጀምር በየወንዙ በየምንጩ በየባህሩ ሲጥልበት ጊዜ ውሃው ተመረዘ፡፡ ያን ውሃ የጠጣ ሁሉ ማበድ ጀመረ፡፡ ሲል ሲል እብደቱ እየባሰ ሄደ፡፡ የእብደት ብዛት እየገነነ ሄደ…ሁሉም ውል አልባ ሆነ፡፡ አገሩ ሁሉ ዝብርቅርቁ ወጣ፡፡ ከዚያም ህዝቡ ተሰባሰበና “ነጋሪት ምንድነው? ቆሪ እንጨት አይደለምን?” መለከትና እምቢልታስ መስራት ማበጀት ያቅተናልን?” አለና ነጋሪቱንና መለከቱንም እምቢልታውንም አብጅቶ “ንጉሱ ወዴት ነው?” እያለ ወደ ቤተ መንግስቱ መትመም ጀመረ፡፡ ንጉሱም በጣም ፈርቶ የግቢውን በር ሁሉ አስዘጋ፡፡ ህዝቡም “ደግሞ ዘግቷልን እኛ አብደን እሱ ሊተርፍ አስቧልን?” እያሉ በሩን የድንጋይና የዱላ መዓት አወረዱበት፡፡
ንጉሱም ይሄንን ባየ ጊዜ ፈላስፋውን “አንተ እነዚህ እብዶች ሊገድሉን ደረሱብን እኮ፡፡ ምን ይበጀን ትላለህ?” በማለት ያማክረዋል፡፡
ፈላስፋውም “እኔማ ከእብደት የሚያተርፈውን ምክር መክሬ ነበር፡፡ ህዝቡ አልሰማ ብሎ ውሃውን ጠጥቶ እንዲህ ከሆነማ ምን እናደርጋለን፤ ያን የሚያሳብደውን ውሃ ጠጥተን ያው እኛም እነሱን መምሰል ነው እንጂ” አለ፡፡ የሚያሳብደውን ውሃም ከተዘጉበት በድብቅ እንዲመጣ በማድረግ ሁሉም በአንድ ላይ ጠጡ፡፡ ወዲያውም ንጉሱና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሁሉ አበዱ፡፡ ንጉሱም እየዘለለ እየቀባጠረ ወዲያው ወደ ግቢው በር ሄደና “ይሄንን በር ማናባቱ ነው የዘጋው?” አለ እርሱ ራሱ ዝጉ ብሎ አስዘግቶ ሲያበቃ፡፡ በሩ ላይ ተሰብስቦ የነበረው ህዝብም ቧ አድርጎ ከፈተለትና ንጉሱ እያበደ እየዘለለ እነርሱን መስሎ በወጣ ጊዜ ህዝቡ ሁሉ መንገድ ለቅቆ ዳርና ዳር ገለል አለና በአንድነት “እልል!” አሉ፡፡ ገሚሱ ያልሰማውም “ምንድር ነው ነገሩ?” ብሎ ሲጠይቁ “ንጉሳችን አብደው ነበር ሽረዋል” ተባለ፡፡ ህዝቡ በድጋሜ ዳር እስከ ዳር እልልታውን አቀለጠው፡፡ በዚህ መልኩ ክፉውን ዘመን ሁሉ እያበዱ ኖሩ፡፡ ደህናው ዘመን ሲገባ ሁሉም እየስፍራው፣ እየሙያው፣ እየምድቡ ገባ፡፡ መንግስቱም አገሩም ሁሉም ረጋ፡፡
ምንጭ፡- ሜጀር ጀ. ኤዲ፡- “ኢን አምሃሪክ ሪደር” (1924 ዓ.ም)

 

ይበል ካሳ

Published in መዝናኛ

በአንድ አገር የኢኮኖሚ እድገትም ሆነ የቴክኖሎጂ ሽግግር ውስጥ የተማረና የሰለጠነ የሰው ኃይል ወሳኝ ነው፡፡ ይህ የሰው ኃይል የሚፈለገውን ውጤት ያስገኝ ዘንድ ከንድፈ ሀሳብ ትምህርት ባለፈ በተግባር የተደገፈ ሥልጠና ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ቀዳሚዎቹ ሲሆኑ፤ እነዚህ ተቋማት ከኢንዱስትሪዎች ጋር በሚፈጥሩት ትስስርም ሰልጣኙ የበለጠ ተግባራዊ ልምምድ እንዲያደርግ እድል ስለሚሰጥ ብቁ ባለሙያ ለማፍራት ያስችላል፡፡ ይህ ደግሞ የኢንዱስትሪ ሽግግሩን ዕውን ለማድረግ አጋዥ ነው፡፡ እኛም በዛሬው እትማችን በዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ላይ ምን እየተሰራ እንደሚገኝ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘርዑ ሱሙር ጋር ያደረግነውን ቆይታ በሚከተለው መልኩ አቅርበነዋል፡፡
የተቋሙ የስልጠና ለውጥ ሂደት
ተቋሙ ከ15 ዓመታት በፊት ሰርተፊኬት ተኮር የአሰለጣጠን ስርዓት ይከተል ስለነበር አሰልጣኝና ማሽን ካለ ወደ ተቋሙ የሄደን ሰው እያሰለጠኑ ማውጣት ስራ ላይ በማተኮሩ ብቁ የሆኑ ባለሙያዎችን እንዳይፈጠሩ አድርጎ ቆይቷል፡፡ ተቋማቱ ከኢንዱስትሪው ጋር የተራራቁና ተቀናጅተው የማይሰሩ ስለነበሩም ሰልጥኖ የሚወጣው የሰው ሃይልም የኢንዱስትሪ ችግሩን የሚፈታ እንዳይሆን አድርጎት ቆይቷል፡፡ ሆኖም የነበረውን ችግር ለማቃለል ከጀርመን ተሞክሮ መነሻ በማድረግ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበና የገበያውን ፍላጎት ባማከለ መልኩ አዲስ የውጤት ተኮር ቴክኒክና ሙያ ስርዓት ተቀረጸ፡፡
በዚህም መሰረት ከ600 በላይ የሙያ ደረጃዎች ተለይተው ምን አይነት ሰልጣኝ በየትኛው ዘርፍና በምን ያክል ደረጃ እንደሚሰለጥን በተቀመጠው አቅጣጫ አሰልጥኖ ማውጣት ብቻ ሳይሆን፤ ብቁ የሰው ሀይልን ለገበያው ለማቅረብ ሲባል ስልጠናው ከተጠናቀቀ በኋላ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ይሰጣል፡፡ በዚህ ሂደትም ብቃቱ የተረጋገጠው ሲያልፍ የተቀረው ደግሞ ዳግም ጉድለቱን ሞልቶ ብቃቱን እንዲያረጋግጥ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል፡፡ መዛኞችም ከኢንደስትሪ የተውጣጡ ባለሙያዎች በመሆናቸው ሂደቱን ስኬታማ አድርጎታል፡፡ ይህ ማለት ግን ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻሉ የመጡ ችግሮች አልነበሩም ማለት አይደለም፡፡
ከዚህ ለውጥ ጎን ለጎን አጠቃላይ ኢኮኖሚውን ሊሸከሙ የሚችሉ የስልጠና ተቋማት ለመገንባት የተጀመረው ስራ ሌላው ስኬት ነው፡፡ በሙያው የጎለበተና አምራች የሰው ኃይል እንዲያፈሩም የተቋማትን አቅም መገንባትና ራሳቸውን በማስቻል የበኩላቸውን እንዲወጡ እየተደረገ፤ ከኢንደስትሪዎች ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ተመጣጣኝ አቅም እንዲፈጥሩም እየተሰራ ነው፡፡ በመሆኑም የስልጠና ተቋማትን አቅም ከመገንባት አኳያ የሚገነቡት ተቋማት አጠቃላይ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ልማት ዕቅድ መነሻ ያደረጉ እንዲሆኑ ይሰራል፡፡
ከስልጠና ጥራት እንዲሁም የስልጠና ፍላጎቶች ጋር በተያያዘም ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች አሉ፡፡ ሆኖም ቀደም ሲል ከአመለካከት ጋር በተያያዘ ህብረተሰቡም ሆነ ተቋሙ ውስጥ ያሉ አገልግሎት ሰጪዎችም የማይቀበሏቸው ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ተቋማቱ ውጤት ያላመጣ ተማሪ እያሰለጠኑ መሆናቸው ተገቢ ያለመሆኑ መተቋሙ፤ ተማሪዎች ከ10ኛ ክፍል ወደ መሰናዶ የሚያስገባ ብሄራዊ መመዘኛ ውጤት ማምጣት ባለመቻላቸው ወደ ተቋማቱ ገብተው የሚማሩ መሆናቸው ደግሞ በህብረተሰቡ ሲታሰብ ቆይቷል፡፡ በሰልጣኞችም በፍላጎት አለመግባታቸውና ‹‹አፈር አይንካኝ›› የሚል አመለካከት መኖሩ ለስልጠናው ማነቆ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ሰልጣኞች ከታች ጀምሮ በሚኖራቸው ዕውቀትን የመቅሰም ቆይታ ስለ ቀለም ትምህርት እንጂ ለቴክኒክና ሙያ ክህሎትን ያማከሉ ስራዎች አለመሰራታቸው ደግሞ የዚህ ችግር አንድ ምክንያት ነው፡፡ ይህም ከስርዓተ ትምህርቱ ጀምሮ የሚታዩ ችግሮች መኖራቸውን አመለካች ሲሆን፤ ሆኖም ከቴክኒክና ሙያ ውጪ ያደገ አለመኖሩን በመገንዘብ ማሻሻያዎች ማድረግ ተገቢነት ነው፡፡ ምክንያቱም 80 በመቶ የሚሆነውን ዕድገት የሚሸከሙት ከዚሁ ተቋም የሚወጡ በመሆናቸው የተግባር ስራውን የሚያከናውኑ ሙያተኞች ሳይወጡ በርካታ መሀንዲሶችን ማፍራት ብቻ ግብ ካለመሆን ባሻገር የሚጠበቀውን ውጤትም ሊያመጣ አይችልም፡፡
ዘርፉ በአዲስ አበባ ራሱን ችሎ በቆመባቸው ዘጠኝ ዓመታት ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ የነበሩ የአመለካከት ክፍተቶች በመታራማቸውም ዘርፉ ለአገር ኢኮኖሚ አስፈላጊና ሚናውም ትልቅ መሆኑን በመገንዘብ ቁጭት መንፈስ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል፡፡ምንም እንኳን ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት አግኝተውም ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትን ምርጫቸው የሚያደርጉ ሰልጣኞች መኖርም ዘርፉ ውጤት እንዳመጣ ማሳያ ይሆናሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የስልጠና ዘርፎች 42 ሺህ ተማሪዎች ያሉ ሲሆን በዘንድሮ የተቀበለው 23 ሺህ ሰልጣኞችን ነው፡፡በአመለካከት በመጣው ለውጥም የቅበላ አቅም ከማሳደጉ በተጨማሪ ሙያ ብቃት ምዘና የማለፍ ምጣኔውን 72 በመቶ በላይ አድርሶታል፡፡በአጫጭር ስልጠና በተመሳሳይ 90 በመቶ ሆኗል፡፡ይህም የጥራት መገለጫ ተደርጎ ባይወሰድም ቀደም ባሉት ጊዜያት የሙያ ብቃት ማረጋገጫ አስፈላጊ እንዳልነበር ትዞ የነበረው አመለካት መቀየሩንና ሰልጣኞች የስልጠና ቆይታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ብቃታቸውን በማረጋገጥ ወደ ገበያ የመግባት ፍላጎታቸው በማደጉን ለውጤት ተግተው እየሰሩ መሆናቸውን ያሳያል፡፡በዘርፉ በታየው ለውጥ ምክንያትም ዩኒቨርሲቲ የነበራቸውን ቆይታ የጨረሱ ምሩቃን በተመሳሳይ ለተጨማሪ ክህሎት የስራ መፍጠሪያም እንደሆነ በማመን ወደ ተቋሙ ዕውቀት ለመሸመት የሚዘልቁትም ተበራክተዋል፡፡
በዘርፉ የነበረ ያለመመዘን ፍላጎቱ የተቃለለ ቢሆንም ምዘናው ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች እንዲወገዱ ሲነሱ ይሰማል፡፡ከኢንደስትሪዎች ጋር ትስስር ፈጥሮ በቅንጅት መስራት ላይ ችግሮች እንዳሉ በተለያዩ መድረኮች ይነሳል፡፡ይሄን ችግር ከመፍታት አኳያ ከዘርፉ ጋር ተጣምረው የሚሰሩ ኢንዱስትሪዎች ቢኖሩም ትስስሩን እንደ ሸክም የሚቆጥሩ ግን አልጠፉም፡፡በዚህም ሰልጣኞች በተግባር ላይ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮችን እያሳዩ የሚያበቁ እንዳሉ ሁሉ፤ መገልገያ ዕቃዎች እንዳይነካባቸው የሚፈልጉ ኢንደስትሪዎችም ይገኛሉ፡፡ይህም በኢንደስትሪዎች ላይ የሚቀሩም የቤት ስራዎች እንዳሉ አመላካች ሲሆን፤ይህን ለማድረግ እየተሰሩ ካሉ ተግባራትም እንደ አብነት የጀርመን ተሞክሮ መነሻ በማድረግ የሚሰራው ስራ ይገኛል፡፡የሙያ ማህበራት ተደራጅተው የሰው ሀይል ልማቱ፣ ቴክኖሎጂ፣ገበያው ላይና ብልሹ አሰራሮችንም ጭምር እንዲታገሉ ለማስቻል የሙከራ ስራው ተጀምሯል፡፡
ኢንደስትሪው በአጭር ጊዜ ውስጥ መሪነቱን ተቀብሎ የአገሪቱን ኢኮኖሚ የማንቀሳቀስ አቅምን ይፈጥራል ማለት ባይቻልም በሶስተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እስከ 2017 ባለው ጊዜ ግን ደረጃውን ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ለዚህም መንግስት ኢንደስትሪው የሚፈለገው ደረጃ ላይ እንዲደርስ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
የድጋፍ ሂደት
በትግራይ ክልል በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፉ የተሻለ ውጤት ያላቸው ተማሪዎች ቓላሚኖ/የተሻለ ውጤት ያላቸው ተማሪዎች ተመርጠው የሚገቡበት ትምህርት ቤት/ እንዲገቡና ምርምር ላይ እንዲሰሩና ሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ የላቀ አስተዋፅዖ እንዲኖራቸው ይደረጋል፡፡በዚህም የተወሰነ ማሻሻል ተደርጎባቸው ህብረተሰቡ ጋር ተደራሽ ቢደረጉ ችግር ፈቺ የሆኑ በርካታ ቴክኖሎጂዎች ይፈልቃሉ፡፡ተኮርጀው ሲሰሩና ተሻሽለው ሲያወጡም ይታያል፡፡በአዲስ አበባም ከ10ኛ ክፍል ወደ ተቋሙ ሲቀላቀሉ የሚሰሩ በርካታ ስራዎች አሉ፡፡
የተለያዩ የቴክኖሎጂ ስራዎችን የሚያወጡ ሰልጣኞች አስፈላጊው ድጋፍ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ይታመናል፡፡ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን ስራቸው ጥቅም ላይ ሳይውል መክኖ ይቀራል፡፡መንግስትም ይህንን ከግንዛቤ ውስጥ በመክተት በከተማ ደረጃ የመለስ ዜናዊ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ፈጠራ ማዕከል ተገንብቶ የማደራጀት ስራው እየተሰራ ነው፡፡
የማህበረሰብ አገልግሎት
ከፍተኛ የትምህርትና ስልጠና ተቋማት በትኩረት ከሚያከናውኗቸው ተግባራት መካከል የማህበረሰብ አገልግሎት ነው፡፡ ዘርፉም ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን ከመደገፍ ጀምሮ በማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎችን በተለያዩ ስልጠናዎች የማሳተፍና የማብቃት ስራውን ይሰራል፡፡በዚህም ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በማውጣት ትርጉም ያለው ለውጥ አምጪ ስራ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
የጥቃቅንና አነስተኛ ስትራቴጂ ከወጣ በኋላ የኢንደስትሪያል ኤክስቴንሽን ድጋፉን ሙሉ በሙሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት እንዲደግፉ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡በዚህም በአስተሳሰብ ተቀብሎ ድጋፉን እያደረገ ይገኛል፡፡በዘርፉ ከሚደገፉት 11ሺ በላይ ኢንተርፕራይዞችና 28ሺ በላይ አንቀሳቃሾች 769 ሞዴል ኢንተርፕራይዞች መፍጠር ተችሏል፡፡75 የሚሆኑ ኢንተርፕራይዞችም የወጪ ንግድ በዓለም ገበያ ላይ እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡125 ኢንተርፕራይዞችም ከከፍተኛ ኢንደስትሪዎች ጋር የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸው ደረጃቸውን አሳድገዋል፡፡በዚህም እስከ ኢንደስትሪ አሰልጣኝነት ደረጃ ደርሰው ከታች የሚመጡ ሰልጣኞችን እንዲደግፉና የሚስተዋለውን ችግር እንዲቃለል እየተሰራ ነው፡፡
ድጋፍ በማድረግ ሂደት ውስጥ ከክህሎት፣አቅም ግንባታና የቴክኖሎጂ አቅም ማሻሻያ ላይ ሰፊ ጥረት ተደርጓል፡፡በስራዎቹም ላይ ምንም ዓይነት ክፍያ የማይጠየቅ ከመሆኑ በተጨማሪ በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ ከ300 በላይ ቴክኖሎጂ በመስራት ከ90 በላይ የሚሆኑት ቴክኖሎጂዎችን ለማሸጋገር ተችሏል፡፡የተቀሩትም በቀጣይ የሚሸጋገሩ ቢሆኑም ማስፋት ላይ ግን የሚታዩ ችግሮች አሉ፡፡የተፈጠሩ ሞዴል ኢንተርፕራይዞች ተሞክሮ በመቀመር ለማስፋት ታቅዷል፡፡ነገር ግን ስራው ለዘርፉ ብቻ ሊተው የሚገባው ሳይሆን በሼድ፣በብድርና በማሽን አቅርቦት ላይ የሚስተዋሉ ማቆዎችን ለማቃለል የሚመለከታቸው ሁሉ ሊሰሩ ይገባል፡፡ይህንን ማስፈፀም የሚችልም ዕቅድ በመዘጋጀቱ መግባባት ተፈጥሮበትም ወደ ስራ ስለሚገባ እርስ በእርስ በመተጋገዝና ልምድ በመለዋወጥ ምርታማነትን ለማሳደግ ይሰራል፡፡
ቀጣይ አቅጣጫዎች
በዘርፉ ያሉ መልካም ጅማሮዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ችግሮቹንም ለማቃለል ተቀዳሚው ተግባር የውስጥ አቅምን ማሳደግ ነው፡፡ ተቋማት ከጠባቂነት በመውጣት ችግሮቻቸውን በራሳቸው ለመፍታት የሚያችላቸውን አቅም በመገንባት በሰው ሀይል፣ በአመለካከት፣በአደረጃጀትና አሰራር አቅማቸውን ማሳደግ ላይ በትኩረት ይሰራል፡፡
ኢንደስትሪው ከዩኒቨርሲቲና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ጋር ያላቸው ግንኙነት በላቀ ደረጃ የማጠናከር ሌላኛው ተግባር ሲሆን፤ ኢንደስትሪው ላይ የሚስተዋለው ችግር መቃለል ለስልጠናው ጥራት ረጅም ጉዞ ያስጉዛል፡፡የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ ክምችት ተቋማዊ በሆነ መንገድ በመስራት ከዚህ ቀደም የተሰሩ የቴክኖሎጂ ስራዎች ዳግም ከመሰራት ይልቅ እንዲሻሻሉ የማድረግ ስራው በተመሳሳይ በትኩረት የሚሰራበት ነው፡፡ይህ ሁሉ ከተከናወነ በኋላም ለስራው ስኬት ወሳኝ የሆነው ህብረተሰቡ በመሆኑ የአመለካከት ቀረፃ ላይ ይሰራል፡፡
ህብረተሰቡ ኋላቀር አመለካከቶችን ወደኋላ በመተው ሙያ የክብር መገለጫ መሆኑን መረዳት ይኖርበታል፡፡በፊት ሸክላ ሰሪ ወርቅ ሰሪ በሚል ሲናቁ የነበሩት በዓለም ደረጃ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ማወቅና ግንዛቤ ማሳደግ ላይም መሰራት ይገባል፡፡በአገሪቱ ከሶስት ሺህ ዓመታት በፊት የአክሱም ሀውልትንና ከአንድ ድንጋይ ተፈልፍለው የተሰሩ የእነ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት ቁሳዊ ቴክኖሎጂ የሰሩ የስልጣኔ እጆችም መከበር አለባቸው፡፡በተያያዘ ጥቅም ላይ ሳይውሉና ሳይከበሩ ቀርተው የጠፉ ዕውቀታዊና ሰነዳዊ ቴክኖሎጂዎች ብዙ ናቸው፡፡በአሁኑ ወቅት ሙያ ያለው ሰው የሚከበርበት ጊዜም በመሆኑ ህብረተሰቡ በሚፈለገው ደረጃ ለማስገንዘብ ከተሰራ የመረዳት አቅሙ ከፍተኛ ነው፡፡ነገር ግን በጥልቀት ዘልቆ መግባት ላይ በቀጣይ በትኩረት ይሰራል፡፡

ፍዮሪ ተወልደ

Published in ማህበራዊ

በበለፀጉት አገሮች ጎልቶ የማይታየው በኋላቀር አገሮች ግን ከፍተኛ ማነቆ ሆኖ የሚገኘው የመሰረተ ልማት አገልግሎት ነው፡፡ከመሰረተ ልማቶቹ አንዱ የሆነው የመንገዶችን መገንባት፣መጠገንና በትራፊኩ ዕድገት መጠን በቀጣይነት እያሻሻሉ መሄድ ያስፈልጋል፡፡መንግስትም ይህንን ተገንዝቦ ከፍተኛ ካፒታል በመመደብ የመንገድ ስራን በከፍተኛ መጠን እያከናወነ መሆኑ ይገለፃል፡፡
ከመሰረተ ልማቱ ጎን ለጎን ፅዱ ውብና ማራኪ ለኑሮ ምቹ አረንጓዴ አካባቢን መፍጠር ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ስትራቴጂውም ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቆሻሻ አሰባሰብ እስከ አወጋገዱ በምን መልኩ መሰራት እንዳለበትና የስልጡን ማህበረሰብ መገለጫ መሆኑ ይገልፃል፡፡በተለይም ደግሞ በአሁኑ ወቅት መዲናይቱ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ለማስዋብ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያሳተፉ የፅዳት ዘመቻዎች በየወሩ ተጀምረዋል፡፡ይሁን እንጂ ከዚህ በሚፃረር መልኩ ለችግር እንደተጋለጡ በመግለፅ የተወሰኑ ነዋሪዎች ለዝግጅት ክፍላችን ቅሬታቸውን ይዘው ቀረቡ፡፡በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ነዋሪ የሆኑት አቶ ተክሉ ደስታ እንደሚሉት አካባቢያቸው ከ80 ዓመት በፊት በተሰራ መንገድ ዛሬም ድረስ ይጠቀማሉ፡፡ ነገር ግን የረጅም ዓመታት የመልማት ጥያቄን የአራራት ሆቴል ካራ መንገድ ስራ ፕሮጀክት ይመልሳል ብለው ተስፋ ቢያደርጉም ሌላ ችግር ይዞባቸው እንደመጣ አወጉን፡፡እኛም በቦታው ተገኝተን ያጠናቀርነውን መረጃ እንዲህ ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች
ወይዘሮ እመቤት መንግስቱ በየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ 11 ነዋሪ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ትይዩ ነዋሪነታቸውን እንዳደረጉ የሚገልፁት ወይዘሮ እመቤት 2001 ዓ/ም ላይ አዲሱ ካርታቸው እንደተሰጣቸው ያስታው ሳሉ፡፡ በዛም መሰረት 30 ሜትር ስፋት ያለው ሜትር እንደሚኖርና እያንዳንዱ ህበረተሰብም ለዚህ ልማት በፍቃደኝነትና በደስታ እንደተስማሙ ያስታውሳሉ፡፡ በ2009 ዓ/ም ሚያዚያ ወር ላይ ግን ከዚህ በተለየ መልኩ አዲስ መረጃ ወደ ጆሯቸው ጥልቅ አለ፡፡
በመረጃው መሰረት ዩኒቨርሲቲው እንደማይነካና መንገዱ የሚነካው ሙሉ በሙሉ ህብረተሰቡን ብቻ እንዲሆን መደረጉን ይገልፃል፡፡በዩኒቨርሲቲው ጥያቄ ለውጡ መደረጉን የሚናገሩት ወይዘሮ እመቤት ቀድሞ መንገዱን በተመለከተ የተደረገው የፕላን ማሻሻያ ላይ መንግስት እንዳላወያያቸው ይገልፃሉ፡፡ ለመሻሻሉ ምክንያት የሆነው ዩኒቨርሲቲው ከአጥሩ በጥቂት ርቀቶች ላይ ላይብረሪና ጂምናዚየም እንዲሁም የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች መኖራቸውን በመግለፁ ነው ይላሉ፡፡በአጥሩ አቅራቢያ ረጅም ዕድሜን ያስቆጠረ ለዘመናት ያገለገለ በሲሚንቶ የተሰራ የውሀ ማጠራቀሚያ እንደሚገኝ ነዋሪዋ ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ዘመን ከ60 ዓመት በፊት በተሰራ ማጠራቀሚያ ተማሪዎች የመጠጥ ውሃ መቅረቡም በተማሪዎቹ ጤና ላይ የሚኖረው ችግርም እንደ ሚኖር ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡
ከመንገዱ ፕላን መሻሻል ጋር በተያያዘ ዋናው ምክንያት ከዩኒቨርሲቲው ዘወትር የሚለቀቀው የመፀዳጃ ቤት ቆሻሻ ፍሳሽ ነው ባይ ናቸው፡፡ ተቋሙም ይህን የአደባባይ ሚስጥር የሆነውን ቆሻሻ ምንጭ ለመደበቅ በማሰብ የማሻሻያ ጥያቄ እንዳቀረበም ይገልፃሉ፡፡በዚህም ተቋሙ ችግሩንም መቆጣጠርና ውሳኔ መወሰን ባለመቻሉ ህዝቡን ለመፈናቀል ሊዳርጉት ነው ይላሉ፡፡የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ ወደ ቤት ውስጥ እየገባ ወደነዋሪዎች ቤት እየገባና በመንገድ እየሄደ እንዲሁም ትራንስፖርት እንኳ ቆሞ መጠበቅ የማይቻልበትን ሁኔታ ህብረተሰቡን የታገሰበት ዋነኛ ምክንያት መፍትሄ ይመጣል በሚል ተስፋ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን ጭላንጭሏ ተስፋ ተዳፍናለች በማለት በውሳኔው እጅግ ማዘናቸውን ይገልፃሉ፡፡
እንደ ወይዘሮ እመቤት ገለፃ፤ፕላን ማሻሻያ በመደረጉ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቤተሰብ አባላት ተጎጂ ይሆናሉ፡፡ተቋሙ እስከዛሬ ቆሻሻውን ባልተገባ ሁኔታ ሲለቅ ህብረተሰቡ ችሎ ቁጭ ያለው መንገዱ መፍትሄ ሊሰጠው ይችላል ከሚል ተስፋ በመነጨ ነው፡፡ነገር ግን አጥጋቢ ባልሆነ ምክንያት የተወሰነው ውሳኔ ተስፋ የተጣለበት መንገድ ጭራሽ ተጎጂ የሆኑትን ህብረተሰቦች ለችግር መንግስትንም ላልተጠበቀ ወጪ የሚዳርግ ነው፡፡በአሁኑ ወቅት ያለው አጠቃላይ መንገድ ስፋት 28 ሜትር ሲሆን የሚሰራው ደግሞ 30 ሜትር ነው፡፡ በዚህም መሰረት ከህብረተሰቡና ከተቋሙ አንድ ሜትር ይነካ የነበረ ቢሆንም ማሻሻያው ግን ሙሉ በሙሉ ህብረተሰቡን የሚነካ መሆኑ መንገድ ስፋቱንም ከ30 ሜትር ወደ 40 ከፍ እንዲል ያደርገዋል፡፡
ነዋሪው የአከራይ ተከራይ ክፍያ የነጋዴው የስራ ግብር ክፍያ ብሎም ከዚህ የተነሳውን ህዝብ ተለዋጭ ቦታ መፈለግም ሌላ ራስ ምታት መሆኑን ይናገራሉ፡፡መንገዱ መጀመሪያ ከታሰበለት ወጪ በላይ ማውጣትም መንግስትን ለኪሳራ ይዳርገዋል ይላሉ፡፡ምንም እንኳን ህብረተሰቡ ለልማቱ ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖረውም ይህን መሰል ማህበረሰቡ ያላመነበትን ስራ መስራት ግን ህዝቡ ልማቱን አምበት ሳይሆን እየተበሳጨ እንዲቀበለውና ቀጣይም በልማቱ ላይ የእኔነት ስሜትን ከማስተጋባት ይልቅ ቸልተኝነትን ያነግሳልም በማለት በእያንዳንዱ ልማት ላይ የህብረተሰቡ ተሳትፎ መኖርና አሳምኖ ማሰራት ለዘላቂ ልማት ያለውን ፋይዳ ይገልፃሉ፡፡
በዩኒቨርሲቲው የሚማሩት የማህበረሰቡ አንድ አካል ልጆች ወንድምና እህቶች በመሆናቸው ለቆሻሻውም ቢሆን የጋራ መፍትሄ መፈለግ ይገባል፡፡ህብረተሰቡም በጉልበቱ፣ በዕውቀቱ ያለውም በገንዘቡ ለመደገፍ ፍቃደኛ ነው፡፡ከዚህ ቀደም ነፍሰጡር ሴቶች ህሙማን በአቅራቢያቸው ወዳሉ የጤና ተቋማት ለማምራት መንገዱ ምቹ ባለመሆኑ በአንዳንድ የገጠሪቱ አካባቢዎች እንደሚስተዋለው በጭንቅ ጥብ ይደርሱ እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡ ህዝቡም ላለፉት ዓመታት ያለፈበትን ችግር ጠንቅቆ ያውቅ ስለነበር በመንገድ ስራ ምክንያት የሚቀነስበትን ሲሰማ ማንገራገር አልታየበትም፡፡ዩኒቨርሲቲውም ይህንን ተቀብሎ መስራት ይኖርበታል፡፡በመሆኑም ህዝቡ ላይ ጫና ከማድረግ ይልቅ ለከተማዋ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ተቋም በመሆኑም ቅድሚያ ለችግሩ መፍትሄ ማስቀመጥ ይጠበቅበታል፡፡
ሌላኛው ነዋሪ አቶ እዮብ ታደሰ ችግሩ በመሰረታዊነት የመልካም አስተዳደር መሆኑን ያመላክታሉ፡፡በመንገድ ስራው ከይዞታው ላይ እንደሚነካበት ህብረተሰቡ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡በዚህ ዙሪያ በተደረገ ውይይትም ለልማቱ መሳካት በጋራ መግባባትና በህብረተሰብ ተሳትፎ እንደሚሰራ መተማመን ተፈጥሮ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ይሁን እንጂ በውይይት መድረኩ ከተባለው ውጪ ህብረተሰቡ ምንም ሳያውቅ ፕላኑ መሻሻሉን መረጃ እንደደረሳቸውና ዕውነታነቱን ለማረጋገጥ ወደሚመለከተው አካል ሲያቀኑም ትክክል መሆኑ ተገልፆላቸዋል፡፡
ፕላኑ የተለወጠበት ምክንያት ህብረተሰቡ ቢያነሳም ጆሮ ሰጥቶ ለጥያቄው ተገቢውን ምላሽ የሚሰጥ አካል ግን አለማግኘታቸውን አቶ እዮብ ያስረዳሉ፡፡ምክንያቱን ለመጠየቅ በቅርብ ከሚያስተዳድረው ወረዳ ቢያመሩም አንዳች መረጃ እንደሌላቸው ክፍለ ከተማም በተመሳሳይ በጉዳዩ ላይ ጠለቅ ያለ ዕውቅና እንደሌለውና ‹‹ቀይሩ ተብሎ መጣልን››የሚል ምላሽ መሰጠቱ ነዋሪውን በቅርብ የሚስተዳድረው ወረዳም ለውሳኔው ባይተዋር መሆኑን ይናገራሉ፡፡የሚመለከታቸው አካላት ሲጠየቁም አጥሩ መነካቱ የቆሻሻ ማጠራቀሚዎቹ ፈንድተው አካባውን ሊያጥለቀልቁ እንደሚችሉ ያላቸውን ስጋት ተገልፆላቸዋል፡፡ታዲያ በቀጣይስ ይህ ማጠራቀሚያ ፈንድቶ ከቅርብ ጊዜ በፊት በቆሻሻ ናዳ ለህልፈተ ህይወትና ለሌሎች ቀውሶች የተዳረጉ ህብረተሰቦች ዕጣ ፈንታ በአካባቢው ህብረተሰብ ላይ ላለመፈጠሩ ምን ዋስትና ይኖራል?ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት ቆሻሻውን ከመልቀቅም አልቦዘነምና ምንስ የተለየ ነገር አለው?ሲሉም ይሞግታሉ፡፡
የመንገድ ስራውን ያስቀየሩት የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች አገልግሎት መስጠት የጀመሩት ከ70 ዓመታት በፊት ነው፡፡ተቋሙም ቆሻሻው በግልፅ የሚሄድበትን መስመር እንደማያውቀው ይገልፃል፡፡ ህብረተሰቡም የቆሻሻውን ሽታና በዚህ የሚደርስበትን የጤና እክልም ለረጅም ዓመታት ችሎ ቆይቷል፡፡ወረዳውም ከአቅሙ በላይ እንደሆነ እንደሚገልፅና በዚህም ነዋሪውም ሆነ የአስተዳደር አካሉ ችግሩን እንደተላመዱትና ተስማምተው እንደሚኖሩ ይናገራል፡፡
የመልካም አስተዳደር ችግር ለማቃለል በየጊዜው በሚሰራ ስራ ይህንን የህብረተሰብ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ መሰጠት ባለመቻሉም በአሁኑ ወቅት የመንገድ ስራው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል ባይ ናቸው፡፡ተቋሙ የህግ የበላይነትን ተላልፎ በፈጠረው ችግር መንግስትም ዋጋ ሊያስከፍለው ተዘጋጅቷል፡፡ በዚህም የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የህብረተሰቡን ቅሬታ ካደመጠ በኋላ አስፈላጊውን ማጣራት አድርጎ ፕላኑ አለመቀየሩን በደብዳቤ እንዳሳወቃቸው ይናገራሉ፡፡ደብዳቤውም በግብዝነት ህብረተሰቡን በደስታ ለሙመላት ታስቦ ሳይሆን ይልቁንም ኮሚሽኑ አምኖበትና ባለሙያዎችም መርምረውት የተፃፈ መሆኑን አፅዕኖት ይሰጣሉ፡፡በሂደቱም ህብረተሰቡ ችግሩን የማወያየት ስራ ቢሰራ በዕምነት ይዞት እንደሚሄድ ከመገንዘብ ይልቅ ጉዳዩ በዝምታ ተይዟል ይላሉ፡፡
ዩኒቨርሲቲው ችግሩን የማይፈታ አድርጎ በማሰብ አማራጮችን ከመፈለግ ይልቅ መንግስትንም የተሳሳተ ውሳኔ እንዲወስን አስችሎታል ይላሉ፡፡አካባቢው ተዳፋታማ በመሆኑ ተቋሙ ባለማፍረሱ ሙሉ በሙሉ ህብረተሰቡ ሲያፈርስ መከላከያ ግንብና ተጨማሪ መንገድም ሊያስፈልግ እንደሚችል ከመንገዶች ባለስልጣንም እንደተገለፀላቸው ያነሳሉ፡፡ይህ ተጨማሪ ወጪም ቀድሞ የነበረውን በዕጥፍ ሊያበዛው ሰእንደሚችል ከዚሁ ጋር በተያያዘ ካሳ ክፍያውና ተለዋጭ ቦታ መፈለግም ሌላው ያልታሰበ ወጪ መሆኑናቸውን ያመላክታሉ፡፡ ተቋሙም ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት ለማድረግ ፈቃደኛ ቢሆን ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ያስችላል እንደ አቶ እዮብ ገለፃ፡፡
ከዚህ ቀደም በ2009 ዓ/ም በዚሁ ጉዳይ ላይ በተፈጠረ መድረክ ውይይት ሲደረግም ከጉዳዩ ጋር ቀጥታ ግንኙነት የሌላቸው ጥበቃ በዩኒቨርሲቲው መላካቸው ለችግሩ ያላቸውን ዕይታ አመላካች ይሆናል፡፡ይህም በርካቶችን የሚያፈራ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም በስነምግባር ብቁ ሳይሆን እንዴት ሌሎችን ሊያበቃ ይቻለዋል የሚል ጥያቄንም ያስነሳል፡፡በቆሻሻ ህብረተሰቡ ሲሰቃይ መቆየቱ ሳያንሰው በተሳሳተ ውሳኔ ደግሞ ህበረተሰቡ ያላግባብ ይዞታው ሊነካበት መሆኑን ያመላክታሉ፡፡
ወረዳው
የወረዳው ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሀይሌ ንጉሴ እንደሚያስረዱት ህብረተሰቡ ፕላኑ አለአግባብ እንዲሻሻል ተደርጓል በሚል ቅሬታ ማቅረባቸውን ይናገራሉ፡፡ ቅሬታ ማቅረባቸውም ሚዛናዊና ባላመኑበት ጉዳይ ላይ መግባባት እንዲቻል መድረክ ተፈጥሯል፡፡ በከተማ ደረጃም ችግራቸው እንዲታይ ተደርጓል፡፡ ዩኒቨርሲቲውም ያሉበትን ችግሮች ለከተማ አስተዳደሩ አቅርቦ የመጨረሻ ውሳኔ ተሰጥቶበታል፡፡ በዚህም መወሰድ ያለበት መንግስት ህብረተሰቡን የሚጎዳ ውሳኔ እንደማይወስን መሆኑ ነው፡፡ በቀጣይም ገዢ የሚሆነው ህጉ ማሳመን የሚችልበት ደረጃ ድረስ ተፈፃሚ እስኪሆን መብታቸውን እንዲጠይቁ መግባባት ተፈጥሯል፡፡
ዩኒቨርሲቲው
የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና እንደሚናገሩት፣ ተቋሙ ልማቱን ቢደግፍም የህብረተሰቡ መጠቀሚያ መፍረስ አለበት የሚል አቋም የለውም፡፡ ነገር ግን የ70 ዓመታትን ዕድሜ ያስቆጠረው ተቋሙ ለዘመናት መፀዳጃ ቤትና ፍሳሾች የተጠራቀመባቸው ማጠራቀ ሚያዎች በአጥሩ አቅራቢያ ይገኛሉ፡፡ የመንገድ ዝርጋታው ሲከናወን ማጠራቀሚያዎቹ ፈንድተው ህብረተሰቡን ያጥለቀልቃሉ፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ሊመጣ ከሚችለው አደጋ ህብረተሰቡን ለመታደግ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ ተቋሙ ሃሳብ አቅርቧል፡፡ ከቆሻሻ ማጠራቀሚዎቹ በተጨማሪም የውሃ ማጠራቀሚያ የሚገኝ በመሆኑ ይህ ሲቋረጥ ከመላው የአገሪቱ አካባቢዎች ዕውቀት ገበታ ለመቋደስ የመጡት ተማሪዎች የሚደርስባቸው ችግር ይኖራል፡፡ በመሆኑም ተማሪዎቹም ሆነ ተቋሙ የህብረተሰቡ አካላት በመሆናቸው ቅድሚያ ጋኑ ቦታ ሊበጅለት ይገባል፡፡
ለዘመናት አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩት ጋኖች የውሃ መስመራቸው የኤሌክትሪክ መስመሩ የማይታወቅ በመሆኑ ቅድሚያ መፍትሄ ሊያገኙ የሚገባቸው ስራዎች መሆናቸውን መገንዘብ ተችሏል፡፡የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎቹም ህብረተሰቡ ላይ እየፈሰሱ ችግር እየፈጠሩ ህዝቡም ቅሬታውን ሲያቀርብ ከ15 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡መሆኑን ለመሸሸግ አልወደዱም፡፡በተያዘ በመንገድ ስራው ምክንያት መናጋት ተፈጥሮም ሊፈነዱ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ሳይገልፁ አላለፉም፡፡በአሁኑ ወቅት ላለው ችግር ግን መንግስት ህዝባዊ ጠቀሜታውን አይቶ ግራና ቀኙን ቃኝቶ ውሳኔው እንደሚወስን ዕምነት እንዳላቸው ይገልፃሉ፡፡ተቋሙ ያለህብረሰቡ ዋጋ የሌለው በመሆኑና ማህበረሰብ አገልግሎትም አንዱ በመሆኑ በቀጣይ ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶችንም በማውጣት በእያንዳንዱ ተግባር ከህብረተሰቡ ጎን ሆኖ ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
መንገዶች ባለስልጣን
በመንገዶች ባለስልጣን የዲዛይንና ክፍል ቡድን መሪ አቶ ጥበቡ አረጋ እንደሚያ ብራሩት፤ባለስልጣኑ ፕላን የመለወጥም ሆነ የማሻሻል ስልጣን የለውም፡፡ነገር ግን በማስተር ፕላኑ መሰረት ባለስልጣኑ ዲዛይን ሰርቶ ለስራ ሲወረድ ዩኒቨርሲቲው ተቃውሞ አቀረበ፡፡ በማሻሻያ ጥያቄውም የመማር ማስማሩን ያውካ የተባሉ ጉዳዮች ተነሱ አስተዳደሩም ጥያቄውን አይቶ ሌላ ዲዛይን በባለስልጣኑ ተሰርቶ ቀረበ፡፡የተሻሻለው ዲዛይን በመፅደቁም ባለስልጣኑ ይህንን ተቀብሎ መንገዱን በፍጥነት ሰርቶ አገልግሎት ላይ እንዲውል ይሰራል፡፡
እኛም በዚህ ላይ ይህ የዲዛይን ማሻሻያ መደረጉ መንግስትን ላልተፈለገ ወጪ አይዳርገውምን? ምን ያክልስ ተጨማሪ ወጪ መጣበት የሚለውን ጥያቄ በባለስልጣኑ የመንገድ ግንባታ ኮንትራት አስተዳደር ዳይሬክተርና የሬጉላቶሪ ዘርፉ ተጠባባቂ ምክትል ዳይሬክተር ኢንጂነር አብርሃም ኤፍሬም አነሳንላቸው፡፡ እንደ ኢንጂነር ኤፍሬም ገለፃ ስራው ላይ የተወሰነ ማሻሻያ መደረጉ መንገዱ ላይ ርዝማኔና ተጨማሪ ወጪ እንዲኖር ያደርጋል፡፡
ፕላን ኮሚሽን
በአስተዳደሩ ፕላን ኮሚሽን የስርፀትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ንጉሴ እንደሚሉት፤በአካባቢው የሚስተዋለውን የትራፊክ ፍሰት ችግር ለማቃለል መሪ ፕላኑ በአካባቢው መንገድ እንዲሰራ አስቀምጧል፡፡ነገር ግን ከነዋሪዎች ቅሬታዎች መጥተዋል፡፡በዚህም የሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በተገኙበት ጉዳዩን በዝርዝር ታይቷል፡፡በዚህ መሰረትም ሁለት አማራጭ ተቀምጠዋል፡፡በአማራጭ አንድ መንገዱ በመሪ ፕላኑ መሰረት ቢሰራ የሚነኩት 27 ቤቶች ብቻ ናቸው፡፡ነገር ግን የዩኒቨርሲቲው የፍሳሽ ማጣሪያና ማጠራቀሚያዎች ችግር ውስጥ እንደሚገባ በባለሙያዎች ተረጋግጧል፡፡
በሁለተኛው አማራጭ ደግሞ መንገዱ ሲሰራ ሊኖር የሚችለው አደጋ ስጋት ለማቃለል መንገዶች ባለስልጣን አስፈላጊ መዋቅራዊ ድጋፍ ስለሚያደርግ ስጋቱ ይቀንሳል፡፡ነገር ግን ቀድሞ ይነኩ የነበሩት ቤቶች በቁጥር ጨምረው 61 እንደሚደርሱ ታውቋል፡፡ የመንገድ ስራው ተጀምሮ ዩኒቨርሲቲው አካባቢ ወደ ስራ መግባት አለመቻሉ በአሁኑ ወቅት የትራፊክ ፍሰቱ ላይ ፈተና እየሆነ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ችግሩን ያቃልላል የተባለው ሁለተኛው አማራጭ ሲወሰድ በግብታዊነት የተወሰደ ሳይሆን በአዋጁ መሰረት ነው፡፡በሐምሌ ወር የፀደቀው የአዲስ አበባ ፕላን ማፀደቂያ አዋጅ አንቀፅ 34 መነሻ በማድረግ ነው፡፡በዚህም የመዋቅራዊ ፕላን ማሻሻያ በቀረበው ጥያቄ አግባብነት መሰረት ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው እንደሚያስረዱት፤ መንገዱ ከፍተኛ የህዝብ ጥያቄ ያለበትና ለበርካታ አመታት እንዲሰራ በተለያዩ መድረኮች ጥያቄ ይቀርብ ነበር፡፡የትራፊክ ፍሰቱም ከፍተኛ ጫና አለበት፡፡መንግስትም የህብረተሰቡን ጥያቄ ወስዶ በከተማዋ ማስተር ፕላን መሰረት መንገዱን ለመስራት ውለታ ሰጥቶ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ስራው ከተጀመረ በኋላም አብዛኛው ህብረተሰብ እጅግ ተባባሪነቱን እያሳየ ይገኛል፡፡የመልማት ፍላጎት እንዳለውም በተግባር እያሳየ ይገኛል፡፡
መንገዱ በፍጥነት እንዲጠናቀቅም ከፍተኛ ስራ እየተከናወነ ነው፡፡በዚህም ምንም እንኳን ስራው በተያዘው 2010 ዓ/ም ቢጀመርም በርካታ ተግባት ተጠናቀው ወደ ስራ ተገብቶ በተሻለ ፍጥነት እየተሰራ ነው፡፡በ2011 ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው መንገድ ስራ በመካከል ላይ ግን ዩኒቨርሲቲው ጋር ሲደርስ ቅሬታ አጋጥሞታል፡፡ ይህም በነበረው ፕላን መሰረት ለመስራት አዳጋች እንደሆነ ማየት ተችሏል፡፡በዚህም በተቋሙ አጥር አካባቢ የፍሳሽ ማስወገጃ የውሃ ፓንፖች መኖራቸው በመታወቁ ይህን አልፎ ፕላኑን ተግባራዊ ማድረግ አልተቻለም፡፡ በመሆኑም ጉዳዩ በጥልቀት ከተመረመረ በኋላ የፕላን ማሻሻያ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ፕላን ማሻሻያ የተደረገውም በደፈናው ሳይሆን የተለያዩ አማራጮች ለማየት ተሞክሮ ነው፡፡በዚህም አሁን ባለው ሁኔታ ፕላኑን ከማሻሻል ውጪ ሌላ የተሻለሰ አማራጭ አለመኖሩን መገንዘብ ተችሏል፡፡በመሆኑም የፕላን ማሻሻያው በሚመለከተው አካል ፀድቆ ወደ ስራ ከተገባ በኋላ አላግባ ነው በሚል ህብረተሰቡ ቅሬታቸውን አቤት አሉ፡፡ይህን ቅሬታቸውንም አፈጉባዔ ፅህፈት ቤት አስገብተዋል፡፡ በዚህም ዩኒቨርሲቲውን ለማዳን ሲባል ብዙሃን የህብረተሰብ ክፍል የሚጎዳ ውሳኔ በመሆኑ እንዲታይ በማለት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡
አስተዳደሩም ህብረተሰቡ ያነሳውን ጥያቄ በማክበርና በመቀበል ሌሎች አማራጮች እንዳሉ ለመመልት ስራ እንዲቆም ተደርጓል፡፡ይህም አስተዳደሩ ዜጎች እንዲጎዱ ምንም ዓይነት ፍላጎት እንደሌለው ያሳያል፡፡ይህንንም መሰረት በማድረግ በድጋሚ በቦታው ተገኝቶ ጉዳዩን የሚፈትሽና መፍትሄ የሚያመላክት በከፍተኛ ደረጃ ኮሚቴ ተዋቅሯል፡፡በኮሚቴው የአስተዳደሩ ፕላን ኮሚሽን መንገዶች ባለስልጣን ውሃና ፍሳሽ የመሬት አስተዳደር የክፍለ ከተማው የመሬት ባለሙያዎች በማዋቀር በፕላን ኮሚሽን መሪነት ጉዳዩ በጥልቀት እንዲጠና ተደረገ፡፡
በኮሚቴው ግኝትም በመጀመሪያ ይነካል ከተባለው አንድ ፍሳሽ ማስወገጃ በተጨማሪ አራት ማጠራቀሚያዎች በአጥሩ አቅራቢያ መኖራቸው ማወቅ ተቻለ፡፡ይህም አደጋ እንደሚሆንና እንኳን ተነክቶ ፕላኑ ተሻሽሎም ጥንቃቄ ካልተሞላበት መንገዱ በሚሰራበት ወቅት በሚኖረው እንቅስቃሴ ሊፈነዳ እንደሚችል ስጋት ተቀምጧል፡፡ይህም ፍንዳታ በአካባቢው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ችላል፡፡ በመሆኑም በምንም መንገድ መንካት አይቻልም በሚል ታይቷል፡፡እንኳን በመጀመሪያው ፕላን አሁንም ተጠግቶ ሲሰራ ልዩ ጥንቃቄ ካልተደረገ በቀር የቆዩ ከመሆናቸው በላይ ሊፈነዳ እንደሚችል ምክረ ሀሳብ ቀርቧል፡፡
የቀረበውን መፍትሄ መነሻ በማድረግም ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ሌሎች ማጠራቀሚያዎች ለማስገንባት ሀሳቦች ቢቀርቡም ጊዜ ይወስዳል፡፡ ለግንባታ የሚሆኑት ግብዓቶች በውጭ ምንዛሬ የሚገቡ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ ከዓመት በላይ ይፈጃል፡፡በተመሳሳይ በአሁኑ ወቅት ባለው የምንዛሬ ሁኔታ መሳሪያዎቹን ለማስገባት አስተማማኝ ምንዛሬ የማይገኝበት ሁኔታ ስለሚያመዝን ያለው አማራጭ የመንገድ ስራ ፕሮጀክቱን ማቆም የግድ ይላል፡፡በመሆኑም ካለው የልማት ጥያቄ አንፃር መንገድ ስራው መቋረጥ ስለሌለበት የመጀመሪያው ውሳኔ ተገቢ እንደሆነ ተረጋጧል፡፡በዚህ መሰረትም ፕላኑ ተሸሽሎ እንዲሰራ ተወስኗል፡፡ሌሎች አካባቢዎች እንደሚደረገው ተገቢውን ካሳ መክፈልና ምትክ ቦታ ህግና ስርዓቱ በሚፈቅደው መንገድ መስጠት ቀጣይ ስራ ይሆናል፡፡
እኛም ይህንን እንዳመጥን ይህ ውሳኔ መንግስትን ለተጨማሪ ወጪ አይዳርገውም ስንልሰ ላነሳንላቸው ጥያቄ ምክትል ከንቲባው እንደሚያስረዱት ተጨማሪ ወጪዎች ይኖራሉ፡፡ነገር ግን ይህን ያመጣው ሌላ የተሻለ አማራጭ አለመኖሩ ነው፡፡ በመሆኑም ስራው ትልቅ የህዝብ ጥያቄ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ጋር የተፈጠረውን ችግር በመመሪያው መሰረት ለማቃለል ይሰራል፡፡ከተማ አስተዳደሩም ህብረተሰቡ ጥያቄ በማንሳቱ የመንገድ ስራው እንዲቆም ተደርጎ መፍትሄ ለማፈላለግ የተቻለውን ርቀት ሁሉ መጓዙን ህብረተሰቡ መረዳት እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡
ከቆሻሻ ማጠራቀሚያዎቹ ጋር በተያያዘ አስተዳደሩ ፅዱና ውብ አካባቢን ለመፍጠር እየተጋ ባለበት በዚህ ወቅት ከዩኒቨርሲቲው የሚወጣው ቆሻሻ ህብረተሰቡ ላይ ይፈሳል፡፡መንገድ ስራውም በዚሁ ምክንያት ማጠራቀሚዎቹ ፈንድተው ህብረተሰቡ ላይ ሊያደርሱት የሚችሉትን ችግር ታሳቢ በማድረግ የተወሰነው ውሳኔ ምን ያክል ዘላቂ መፍትሄ ይሆናል፡፡በቀጣይስ ባልታሰበ ሁኔታ ፍንዳታው ላለመከሰቱ ምን ዋስትና አለ በሚል ለአቶ አባተ ጥያቄያችን አነሳን፡፡
ምክትል ከንቲባው ‹‹አያድርስ ነው›› በማለት ዋስትና እንደሌለ ይናገራሉ፡፡በመሆኑም በመንገድ ስራው ምክንያት ችግር እንዳይፈጠር የመከላከያ ግንብ እንዲሰራና መንገዶች ባለስልጣን ኃላፊነቱ ተሰጥቶታል፡፡ስፍራው ሳይነካም ፍሳሹ እየወጣ ህብረተሰቡን እያስቸገረ በመሆኑ ጊዜያዊ መፍትሄ እንዲሆን መከላከያ ድጋፍ ግንብ እንዲሰራ ተወስኗል፡፡በቀጣይ ግን ዩኒቨርሲቲው ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያስቀምጥ መግባባት ተፈጥሯል ይላሉ፡፡
ማጠቃለያ
መንግስት ልማትን ለማረጋገጥ የህብረተሰብ ተሳትፎ ወሳኝነት በግልፅ ያስቀምጣል፡፡ ይሁን እንጂ የአካባቢው ነዋሪዎች አሳታፊነት ላይ ችግር እንዳለና የሚመለከታው አካላት አሳማኝ የሆነ ምክንያት ቢቀመጥ ያለምንም ማገራገር እንደሚቀበሉት ተናግረዋል፡፡እናም ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚመለከታቸው አካላት ቢሰሩ መልካም ይሆናል፡፡ በተመሳሳይ የማህበረሰብ አገልግሎት አንዱ ተግባሩ የሆነው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ቆሻሻ ሲለቅ መመልከት ህግን ከመጣስም ባለፈ ዜጋን ከሚያንፅ ተቋም የማይጠበቅ ነው፡፡በአሁኑ ወቅት ለመንገድ ስራው ሲባል አጥሩን አለመንካቱም ዘላቂ መፍትሄ ካለመሆኑ ባሻገር ቀጣይ በማህበረሰቡ ላይ ሊደርስ ከሚችለው አደጋ መከላከል ስራ መሰራት ይኖርበታል መልዕክታችን ነው፡፡

ፍዮሪ ተወልደ

Published in ፖለቲካ

የአንድ አገር ግብርና አድጓል የሚባለው በዋነኝነት ከዘርፉ የሚገኘው ምርትና ምርታማነት ሲያድግ ነው፡፡ ለዚህም ነው ስለ ግብርና ዕድገት ሲነሳ የአሜሪካ ግብርና ሁሌም በምሳሌነት የሚጠቀሰው፡፡ ምክንያቱም የአሜሪካ ግብርና ከጠቅላላው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚይዘው ድርሻ ሁለት በመቶ ብቻ ሆኖ ሳለ ከዘርፉ የሚገኘው ምርት ግን ከዚያች አገር ዜጎች አልፎ ዓለምን ሁሉ መመገብ የሚችል ሆኗል፡፡ ለምን ቢባል የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ስለተቻለ፡፡ ታዲያ የግብርና ዕድገት ማለት የምርትና ምርታማነት ዕድገት ከሆነ እዚህ ላይ አተኩሮ መስራት የግድ ይላል ማለት ነው፡፡ በተለይም ደግሞ በግብርና ሥራ ውስጥ የሰብል ልማትም ሆነ የእንስሳት እርባታ በሚካሄድበት ወቅት ለሰብሉ ወይንም ለእንስሳው ጤና ቅድሚያ ሰጥቶ መንቀሳቀስ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚሰራውን ሥራ ውጤታማ ያደርገዋል፡፡
ከዚህ አኳያ አስቀድሞ የመከላከል ሥራው እንዳለ ሆኖ ሰብሎችን የሚያጠቁ የተለያዩ ፀረ ሰብል ተባይዎችና በሽታዎች በሚከሰቱበት ወቅት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የፀረ ተባይና ፀረ በሽታ መድኃኒቶች በእጅጉ አስፈላጊ መሆናቸውን በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ይናገራሉ፡፡ ሆኖም የጃካራንዳ ኢንቲግሬትድ አግሮ ኢንዱስትሪ ሥራ አስኪያጅ አቶ ደመላሽ ወጋየሁ እንደሚሉት በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የሰብል መድኃኒቶች እጥረት አለ፡፡ የዓለም የሥነ ምህዳርና የአየር ሁኔታ በእጅጉ ተለዋዋጭ እየሆነ መምጣቱን የሚጠቁሙት ሥራ አስኪያጁ፤ «አሁን ላይ ያለው የፀረ ሰብል ተባይዎችና በሽታዎች ዓይነት እንደ ድሮው አይደለም፤ በጣም በፍጥነት የሚራቡ የነፍሳት ዓይነቶች ነው ያሉት» ይላሉ፡፡
በመሆኑም ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት በመድኃኒት አቅርቦቱ ላይ ትኩረት ተደርጎ ካልተሰራ በሰብል ላይ የሚደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ውድመትን የሚያስከትል ይሆናል፡፡ ከዚህ ቀደም ያሉት ተሞክሮዎችም ይህንን ሁነት በተጨባጭ አመላክተው አልፈዋል፡፡ ለአብነትም በቅርቡ በቲማቲም ላይ ተከስቶ ከፍተኛ ውድመት ያደረሰውን «ቱፓ ሱልካ» የተባለ ተባይ ወረርሽኝ ያደረሰውን ከፍተኛ ውድመት በማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡ የተባይ ወረርሽኙ እንደ ዝዋይ፣ መቂና ቆቃ እንዲሁም የላይኛው አዋሽ በመሳሰሉ በቲማቲም ምርታቸው በሚታወቁ አካባቢዎች ከባድ ጉዳት አስከትሎ አልፏል፡፡ ይህም በቲማቲም ምርት ላይ የተሰማሩ የበርካታ ባለሀብቶችና ገበሬዎችን በመቶ ሺዎችና በሚሊዮኖች ለሚቆጠር ኪሳራ መዳረጉን ያመላክታሉ፡፡ «በእንዲህ ዓይነት ጊዜ ፀረ ተባይ መድኃኒቶች የሚኖራቸው ፋይዳ በእጅጉ የላቀ ነው» የሚሉት ሥራ አስኪያጁ ሆኖም የአቅርቦት እጥረት በመኖሩ ምክንያት በሽታው ከቁጥጥር ውጪ ወጥቶ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ይናገራሉ፡፡ ወለጋና ባኮ አካባቢም በማንጎ ተክል ላይ ተመሳሳይ ችግር በማጋጠሙ ምክንያት በአገሪቱ ያለው የማንጎ ምርት በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ መሆኑን በተጨማሪ ማሳያነት ያነሳሉ፡፡
በቅርቡም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የበቆሎ ሰብልን የሚያጠቃ አደገኛ ተምች ተከስቶ እንደነበር የሚያስታውሱት ሥራ አስኪያጁ ካለው ፈጣንና ተለዋዋጭ የአየር ሁኔታ አኳያ ፀረ ሰብል የተባይ ወረርሽኞች በቀጣይም በማንኛውም ሰዓት ሊከሰቱ ስለሚችሉ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል በቂ የመድኃኒት አቅርቦት ሊኖር ይገባል፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት በአገሪቱ ምርትና ምርታማነት እንዲቀንስ ከሚያደርጉ ችግሮች መካከል አንደኛው ፀረ ሰብል ተባዮችና የሰብል በሽታዎች የሚያደርሱት ጉዳት ነው፡፡ የምርትና ምርታማነት መቀነስ በተራው ዘርፉን በተፈለገው ፍጥነት እንዳያድግ ስለሚያደርግ ግብርናው ለአጠቃላይ ኢኮኖሚው የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ይቀንሰዋል፡፡ እናም በአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖ በቀላሉ ሊታይ አይገባውም ባይ ናቸው፡፡ በመሆኑም ችግሩ በሚከሰትበት በማንኛውም ሰዓት ፀረ ተባይና ፀረ በሽታ የሰብል መድሃኃኒቶቹ በሚፈለገው መጠን ማግኘትና መጠቀም እንዲቻል አቅርቦት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት በምርትና ምርታማነት ብሎም በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ማስቀረት የሚቻልበት ሁኔታ መኖሩን ያመላክታሉ፡፡
አብዛኞቹ ፀረ ተባይና ፀረ በሽታ መድኃኒቶች ከውጭ የሚገቡ መሆናቸውን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ «እጥረት ከመኖሩ በአሻገር መድኃኒቶቹ ቢገኙም እንኳን ዋጋቸው በጣም ውድ መሆኑ ችግሩን አባብሶታል፤ አንዳንዶቹም የጥራት ችግር ያለባቸው በመሆናቸው አገልግሎታቸውም አነስተኛ ነው» ይላሉ፡፡ በመሆኑም በዚህ ዙሪያ ያለውን ችግር ለመፍታት መድኃኒቶቹ አገር ውስጥ የሚመረቱበትን ሁኔታ ማመቻቸት ላይ ትኩረት ተደርጎ ቢሠራ የተሻለ ውጤት ሊገኝ እንደሚችል ያላቸውን አስተያየት ይሰነዝራሉ፡፡ በሰብል በሽታ መድኃኒቶች አቅርቦት ላይ ያለውን ችግር በአግባቡ ለመፍታት ከእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር እንዲሁም ከሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት ግዴታ መሆኑን አንስተው «ሆኖም እስካሁን ባለው አካሄድ እኛም ወደ እነርሱ አልሄድንም፤ እነርሱም ወደ እኛ አልመጡም» ይላሉ፡፡ ሆኖም ይህ የተሳሳተ አካሄድ መሆኑን ጠቁመው፤ ለቀጣዩ ግን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራት እንቅስቃሴ መጀመራቸውንና የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ለማ በበኩላቸው እንደ አንበጣ የመሳሰሉ በራሪ ፀረ ሰብል ተባዮችን የሚቆጣጠራቸው መንግሥት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ለዚህም በያመቱ እንደ አገር በዘር ከሚሸፈነው ጠቅላላ የማሳ መጠን አስር በመቶ የሚሆነውን ሊረጭ የሚችል ፀረ ተባይ ኬሚካል ተገዝቶ በመጠባበቂያነት ይቀመጣል፡፡ ከዚህም በተጨማሪም መንግሥት መደበኛ ፀረ ሰብል ተባዮችን የሚቆጣጠርበት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስልትን መሰረት ያደረገ ራሱን የቻለ የመቆጣጠሪያ ሥርዓት መኖሩን የሚናገሩት የሰብል ልማት ዳይሬክተሩ «ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያዘ ተባዮቹ ድንገት በሚከሰቱበት ወቅት የመድሃኒቶች እጥረት ሊከሰት ይችላል» ይላሉ፡፡
መንግሥት እንደ አገር ከሚይዘው አስር በመቶ መጠባበቂያ የመደበኛ ፀረ ተባዮች የመድኃኒት ክምችት በስተቀር መድኒኃቶቹ የሚቀርቡት በነጋዴዎች አማካኝነት በመሆኑ ነጋዴዎች ደግሞ ሊሸጡ የሚችሉትን መጠን ብቻ አስበው መድኃኒቶችን ስለሚያስገቡ ተባዮቹ በድንገት በስፋት በሚከሰቱበት ወቅት እጥረት ያጋጥማል፡፡ በመሆኑም የፀረ ተባይ መድኃኒቶች አቅርቦትን በተመለከተ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥመው ችግር ድንገተኛ ለሚከሰቱ ተባዮች የሚያስፈልገው የመድኃኒት መጠን ምን ያህል እንደሆነ አስቀድሞ ማወቅ የማይቻል ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
አቶ ኢሳያስ «የግብርና ሚኒስቴር በአገሪቱ ሊከሰት የሚችለውን የፀረ ሰብል ተባይ አደጋ እየተከታተለ ተባዩ በሚከሰትበት ወቅት በግብርና ሥራ ላይ የተሰማራው የህብረተሰብ ክፍል መድኃኒቶችን እንዲጠቀም ሙያዊ ምክር ይሰጣል እንጅ መድኃኒት አቅራቢ አይደለም» ይላሉ፡፡ ሚኒስቴሩ የልማት ሠራተኞች በሚሰጡት ምክረ ሃሳብ መሰረት አስመጭው መድኃኒቶቹን ገዝቶ ሲያቀርብ አርሶ አደሩ ገዝቶ ይጠቀማል፡፡ እነኝህ ፀረ ተባይ መድኃኒቶች ተፈላጊ የሚሆኑት ደግሞ ተባይዎቹ በሚከሰቱበት ወቅት እንጅ በየጊዜው በሚካሄደው መደበኛ የግብርና የሰብል ልማት ጥቅም ላይ ስለማይውሉ አቅርቦታቸው የሚወሰነው ነጋዴው ሊሸጠው በሚችለው መጠን መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ እናም በግብርና ሥርዓቱ ውስጥ የፀረ ተባይ መድኃኒቶች በቀጥታ የሚቀርቡ የግብዓት ዓይነቶች ባለመሆናቸው በቋሚነት ለማቅረብ የማይቻል በመሆኑና ተባዮቹ ድንገት በሚከሰቱበት ወቅትም የሚፈለገው መጠን ምን ያህል መሆኑን አስቀድሞ ለማወቅ አስቸጋሪ በመሆኑ አልፎ አልፎ የአቅርቦት ችግር ይከሰታል፡፡
በአንጻሩ ፀረ- አረም ኬሚካሎችና እንደ ፀረ- ፈንገስ የመሳሰሉ የሰብል በሽታ መድኃኒቶች ከፍተኛ ሽያጭ ስላላቸው አቅርቦታቸው በቂ መሆኑን ያመላክታሉ፡፡ ምክንያቱም እነዚህኞቹ መድኃኒቶች በመደበኛው የእርሻ እንቅስቃሴ ውስጥ ሁሌም ተፈላጊ በመሆናቸው ምርቶቹ ስለሚሸጡለት ነጋዴው በብዛት ገዝቶ ስለሚያቀርባቸው ነው፡፡ ፀረ- ሰብል ተባዮችና የሰብል በሽታዎች ምርትና ምርታማነት በመቀነስ ረገድ አሉታዊ ሚና እንዳላቸው የሰብል ልማት ዳይሬክተሩም በአቶ ደመላሽ ሃሳብ ተስማምተው በቀጣይ ችግሩን ለመፍታት ስትራቴጅ ተነድፎና አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ በአገሪቱ የግብርና ምርት ዕድገት ላይ የሚያሳርፉት አሉታዊ ተፅዕኖ በቀላሉ ሊታይ አይገባውም፡፡ ካለው ፈጣንና ተለዋዋጭ የአየር ሁኔታ አኳያ ፀረ- ሰብል የተባይ ወረርሽኞች በቀጣይም በማንኛውም ሰዓት ሊከሰቱ ስለሚችሉ በመድኃኒቶቹ አቅርቦት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራቱ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና ግብርናውንም ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ እናም እዚህ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራቱ ተገቢም አስፈላጊም ነውና የበለጠ ሊታሰብበት ይገባል እንላለን፡፡

ይበል ካሳ

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።