Items filtered by date: Tuesday, 06 March 2018

የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ካለፈው ሐሙስ እስከ እሁድ ድረስ ለአስራ ሰባተኛ ጊዜ በእንግሊዝ በርሚንግሃም ከተማ ሲካሄድ ኢትዮጵያ አስደሳች ውጤት ማስመዝገብ ችላለች። በቻምፒዮናው አምስት ወርቅ፤ ስድስት ብርና ሁለት ነሐስ አስመዝግባ በአንደኛነት ካጠናቀቀችው አሜሪካ ቀጥሎ ኢትዮጵያ አራት ወርቅና አንድ ብር በማስመዝገብ ከዓለም ሁለተኛ ከአፍሪካ ደግሞ ቀዳሚውን ደረጃ ይዛ ማጠናቀቋ ይታወቃል። ይህም በቻምፒዮናው ታሪክ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ 2008 ስፔን ቫሌንሲያ ካስመዘገበችው አራት ወርቅ፤ አንድ ብርና አንድ ነሐስ በመቀጠል በሁለተኛነት የሚቀመጥ ትልቅ ውጤት ሆኗል።
በዚህ ቻምፒዮና ከተመዘገበው አስደናቂ ውጤት ጎን ለጎን በውድድሮች ላይ የታዩት ተስፋ ሰጪ አትሌቶችና ሜዳሊያዎቹ የተመዘገቡበት ሂደት ሳይደነቅ መታለፍ የለበትም። የተመዘገቡት አራቱ የወርቅ ሜዳሊያዎችና አንድ የብር ሜዳሊያም በዚህ ቻምፒዮና ኢትዮጵያን ያኮራ ብቻ ሳይሆን የነገውን የአትሌቲክስ ጉዞ ብሩህነት ያንፀባረቁ መሆናቸው ሊነሳ ይገባል።
የቻምፒዮናው ኮከብ አትሌት የሆነችው ገንዘቤ ዲባባ ከምንጊዜውም በላይ ያንፀባረቀችበት ውድድር ይህ ነው። ገንዘቤ ቻምፒዮናው ሲጀመር በተካሄደው የሴቶች ሦስት ሺ ሜትር ውድድር 8:45.05 በሆነ ሰዓት የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገበች አትሌት ነች። ገንዘቤ ባለፈው ዓመት መጥፎ ሊባል የሚችል የውድድር ዘመን ከማሳለፏ በተጨማሪ በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የፍፃሜ ተፋላሚ እንኳን መሆን አልቻለችም ነበር።
በትንሽ ወራት ውስጥ ከጉዳት አገግማ በዓለም ቻምፒዮና ኮከብ የነበሩ እንደ ኬንያዊቷ ሔለን ኦቢሪና ሆላንዳዊቷ ሲፈን ሃሰን ዓይነት አትሌቶች ጋር እልህ አስጨራሽ ፉክክር አድርጋ ለዚህ ድል መብቃቷ አስደናቂ ነው። በቻምፒዮናው እጅግ ጠንካራ በነበረው ፉክክር ከመጥፎ የውድድር ዓመት ማግስት ለስኬት መብቃቷም ወደ ፊት በትልቁ የዓለም ቻምፒዮናና ኦሊምፒክ መድረክ ሌላ ስኬት ላይ እንደምትታይ ተስፋ የሰጠ ነው። ዛሬ ባይሳካላት ነገ አዲስ ታሪክ መስራት እንደምትችልም ያሳየችበት ነው። ገንዘቤ ቻምፒዮናው ሲጠናቀቅ በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር 4.05 27 በሆነ ሰዓት ተጨማሪ ወርቅ ያጠለቀችበት አጋጣሚም በርካታ ክብረወሰኖችን እንድትጨብጥ ከማስቻሉ በተጨማሪ በአትሌቷ ብቃት ላይ ጥርጣሬ ያላቸውን ወገኖች እንዲያምኑ ያስገደዳቸው ጭምር ነው።
ገንዘቤ በዚህ ቻምፒዮና ታሪክ እ.ኤ.አ በ1999 ጃፓን ሜባሺ ላይ ኃይሌ ገብረስላሴ በአንድ ሺ አምስት መቶና ሦስት ሺ ሜትሮች ጥምር የወርቅ ሜዳሊያዎች ካጠለቀ ወዲህ ተመሳሳይ ታሪክ ስትሰራ የመጀመሪያዋ አትሌት ሆናለች።
የታላላቅ እህቶቿን ወርቃማ ኦሊምፒያኖች እጅጋየሁና ጥሩነሽ ዲባባ ፈለግ ተከትላ በመካከለኛ ርቀት የስኬት ማማ ላይ የደረሰችው ገንዘቤ ዲባባ እ.ኤ.አ 2012 ቱርክ ኢስታንቡል ላይ በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር 4፡05፡78 በሆነ ሰዓት የመጀመሪያ የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቋ ይታወሳል። ከዚያም በኋላ 2014 ፖላንድ ሶፖት ላይ በሦስት ሺ ሜትር 8፡55፡54 ሰዓት ሁለተኛ የወርቅ ሜዳሊያዋን ማጥለቅ ችላለች።
ባለፈው የ2016 ፖርትላንድ ዩጂን ቻምፒዮናም በሦስት ሺ ሜትር 8፡47፡43 ሰዓት ሦስተኛ የወርቅ ሜዳሊያዋን ከቻምፒዮናው አግኝታለች። የዘንድሮው ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ ሲታከልበትም በቻምፒዮናው ታሪክ አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ትልቅ ታሪክ ካላቸው ከጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴና ከመሰረት ደፋር በላይ ስኬታማዋ አትሌት አድርጓታል።
የመወዳደሪያ ዕድሜው ገና በወጣቶች ጎራ እያለ ከዕድሜ ታላላቆቹ ጋር በታላላቅ የውድድር መድረኮች መካፈል የቻለው አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ ከዚህ ቀደም በርካታ ጊዜ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የነገው ተስፋ እንደሚሆን ተነግሯል። ዮሚፍ ይህንን በተግባር ማሳየት የቻለውም ባለፈው የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ፖርትላንድ ዩጂን ላይ ሦስት ሺ ሜትሩን 7፡57፡21 በሆነ ሰዓት አሸንፎ ወርቅ ሲያጠልቅ ነበር። ዮሚፍ ዘንድሮም ይህን ድሉን 8:14.41 በሆነ ሰዓት ማስጠበቅ ችሏል።
በውድድሩ ላይ ያሳየው ድንቅ ብቃትና በተፎካካሪዎቹ ላይ የወሰደው የበላይነት ከእድሜው አኳያ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ውጤት በጠፋበት አምስትና አስር ሺ ሜትር ቀነኒሳን የሚተካበት ወቅት እንደተቃረበ ማሳያ ነው። በዚህ ውድድር ብቻም ሳይሆን በዋናው የዓለም ቻምፒዮናም ይህን ማሳየት የቻለ አትሌት በመሆኑ ብዙዎች ተስፋ አድርገውበታል።
ዮሚፍ ባሸነፈበት ውድድር የብር ሜዳሊያ ያጠለቀው ወጣት አትሌት ሰለሞን ባረጋም ውጤቱና አስደናቂ ብቃቱ ኢትዮጵያ በቅርቡ በታላላቅ መድረኮች አረንጓዴውን ጎርፍ ዳግም የማየት ብሩህ ተስፋ እንዳላት ማሳያ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እጅግ አስደናቂ ብቃት በማሳየት ጊዜ ሳይፈጅበት በታላላቅ የውድድር መድረኮች ኢትዮጵያን ወክሎ ውጤታማ መሆን የቻለው ሰለሞን ባረጋ ድንቅ የሩጫ ተሰጥኦው ብቻም ሳትይሆን በመካከለኛና ረጅም ርቀቶች በቅርብ ጊዜ ውስጥ ዙፋን ላይ እንደሚወጣ የስፖርቱ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ይመሰክሩለታል።
ዮሚፍና ሰለሞን አሁን ላይ በሦስት ሺ ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር ትልቅ ስኬት ያስመዝግቡ እንጂ ከቤት ውጪ ባሉ ውድድሮች በአምስት ሺ ሜትር የበለጠ ታዋቂና ስኬታማ ናቸው። ይህም የዓለም ቻምፒዮኑ ሙክታር ኢድሪስና ሐጎስ ገብረህይወትን ጨምሮ ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ በታላላቅ የውድድር መድረኮች አስፈሪ ስብስብ እንደሚኖራት ማሳያ ነው።
አራተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ በወንዶች አንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ያስመዘገበው ወጣቱ አትሌት ሳሙዔል ተፈራ፣ የቻምፒዮናው ክስተት ነበር። በርቀቱ ብልጭ ድርግም የሚለውን የኢትዮጵያ ተስፋም ዳግም እንዲያንሰራራ ያደረገ ነው። በታላላቅ የውድድር መድረኮች የማናውቀው ሳሙዔል ተፈራ ድንገት በዚህ ቻምፒዮና ልምድ ያላቸውን አትሌቶች ያሸነፈበት መንገድም ኢትዮጵያ ጠንክራ ከሰራች ስኬታማ እንደምትሆን ያሳየ ነው።
ይህ አትሌት በርቀቱ እ.ኤ.አ ከ2012 ቱርክ ኢስታንቡል ደረሰ መኮንን ካስመዘገበው ውጤት ወዲህ የመጀመሪያው ሲሆን፣ በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ወርቅ ሲያስመዘግብ ከኃይሌ ገብረስላሴና ደረሰ መኮንን ቀጥሎ ሦስተኛው አትሌት ነው።
17ኛውን የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና አሜሪካ በ6 የወርቅ፣ 10 የብር እና 2 የነሃስ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ከዓለም 1ኛ በመሆን ማጠናቀቅ ችላለች።ኢትዮጵያ ደግሞ 4 የወርቅ እና 1 የብር በድምሩ በ5 ሜዳሊያዎች ሻምፒዮናን ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቅ ችላለች።
ከኢትዮጵያ በመቀጠል ፖላንድ 2 የወርቅ፣ 2 የብር እና 1 የነሃስ በድምሩ በ5 ሜዳሊያዎች ሦስተኛ ደረጃን ስትይዝ፤ ብሪታንያ ፈረንሳይ እና ኮትዲቯር ከ4 እስከ 6 ያለውን ደረጃ መያዝ ችለዋል።
ኢትዮጵያ በሰበሰበቻቸው ሜዳሊያዎች ከአፍሪካ አንደኛ ሆና ስታጠናቅቅ፤ 1 የወርቅ እና 1 የብር ሜዳሊያ ያገኘችው ኮትዲቯር ከሁለተኛ፤ ቡሩንዲ በ1 የወርቅ ሜዳሊያ 3ኛ ሆናለች። የኢትዮጵያ የምንጊዜም ተቀናቃኝ ጎረቤት ኬንያ በውድድሩ 1 የነሐስ ሜዳሊያ ብቻ አግኝታ ውድድሩን 24ኛ ሆና አጠናቃለች፡፡

ታምራት ተስፋዬ

Published in ስፖርት
Tuesday, 06 March 2018 17:14

መኪናን በበረዶ

ወዳጆቼ መኪናን በበረዶ ስልዎ መኪናን በበረዷማ አየር ማሽከርከር ብለው እንዳይ ተረጉሙት፡፡ በበረዶ በተሸፈነ የአስፓልት መንገድ ላይ መንዳት ብለውም እንዳያስቡ፡፡ ነገሩ ሌላ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የአውሮፓ አህጉር የአየር ፀባይ በአብዛኛው ቀዝቃዛና በረዷማ ነው፡፡ እኛ አገር ደግሞ በረዶ ቢጥልም በረዶ የማየት አምሮታችንን ሳናጣጥም ወዲያው ከስሞ ወደውሃነት ይቀየራል፡፡ ምን ይደረግ የአየር ፀባያችን የተለያየ ነዋ! በአብዛኛዎቹ የአውሮፓ አገራት ከስድስትና ከዛ በላይ ወራት የበረዶ ወቅት በመሆኑ በረዶን ማየት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በረዶ በእነዚሁ አገራት ውስጥ እንደልብ በመገኘቱም የበረዶ ሸርተቴ የመሰሉ የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮችን ሲያደርጉም ይስተዋላል፡፡
ከአሁን ቀደም ከበረዶ ተቀርፀው የተሰሩ ትላልቅ ቤቶችን አይታችሁ ተደምማችሁ ሊሆን ይችላል፡፡ የኦዶቲ ሴንተራል ዘገባ እንደሚያሳየው ከሆነ ግን፤ የሩሲያዋ ኖቮሲበርስክ ከተማ ነዋሪ ሞተረኛ በበረዶ መኪና በመስራት የሰሞኑ መነጋገሪያ ዜና ሆኗል ይለናል፡፡
ቭላዲስላቭ ባራሼንኮቭ የተባለው የጋራዥ ባለቤት 54 የተቀረፁ የበረዶ ግድግዳዎችን በመጠቀም መረሴዲስ መኪና ለመስራት በቅቷል፡፡ ባራሼንኮቭ መጀመሪያ የመኪናውን አካል በበረዶ ቅርጽ ብቻ እንዳይንቀሳቀስ አድርጎ ለመስራት ሃሳብ የነበረው ቢሆንም፤ በኋላ ላይ ግን ሃሳቡን በመቀየር የወታደር መኪና ላይ በረዶውን በማስቀመጥ መኪናዋን ከበረዶ ሊሰራት ችሏል፡፡ ከበረዶ የተሰራቸውን መኪና ልክ እንደ መደበኛ መኪና መንዳት ቀላል ባይሆንም የሚንቀሳቀስ የበረዶ አካል ያለው መኪና ለመፍጠር ችሏል፡፡
ከበረዶ ቅርፅ የተሰሩትን የመኪናውን አካላት እርስ በርስ እንዲያያዙ ባራሼንኮቭ የተጠቀመበት ማጣበቂያ ምን እንደሆነ እስካሁን ግልፅ ያልሆነ ነገር ቢሆንም፤ መኪናውን በጠፍጣፋ ወይም በማያንገጫግጭ መንገድ መንዳት ችሏል፡፡ ባራሼንኮቭ የመኪናውን አካል በበረዶ ሰርቶ ካጣናቀቀ በኋላም የበለጠ ውበት እንዲኖረው በማሰብ በረዶውን በቀለማማ መብራት አስውቦታል፡፡ ባራሼንኮቭ ከአሁን ቀደምም በበረዶ በርካታ ቅርፃቅርፆችን መስራቱ የሚታወስ መሆኑን ዘገባው ገልፆ፤ የአሁኑ ሥራው ግን የብዙዎችን ቀልብ መሳብና አነጋጋሪ መሆኑን ቀጥሏል ሲል አስፍሯል፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

Published in መዝናኛ
Tuesday, 06 March 2018 17:12

ትዳር አጣማጁ ዛፍ

ሰዎች በስራና በተለያዩ አጋጣሚዎች ከውሃ አጣጫቸው ጋር ሲገናኙ ይስተዋላል፡፡ የትዳር አጣማሪያቸውን እርስ በርሳቸው በመተዋወቅ ማግኘት ባይችሉ እንኳን ዘመኑ ተሻሽሏልና የትዳር አፈላላጊ ኤጀንሲዎች እየበዙ መምጣታቸውን ተከትሎ መፍትሄ የለም ብሎ ተስፋ መቁረጥ ቀርቷል፡፡ በአገራችንም አሁን አሁን ትዳር አገናኝ ኤጀንሲዎች ብቅ በማለታቸው የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ የስልክ ቁጥር በማዘጋጀት በስልክ ጥሪ አማካኝነት ትዳር የሚያፈላልጉና ከትዳር ጋር በተያያዘ መፍትሄ የሚሰጡ ኤጀንሲዎችም እየበዙ መጥተዋል፡፡
ከሰሞኑ ኦዲቲ ሴንትራል የተሰኘው የመዝናኛ ድረ ገፅ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ትዳር አጣማጅ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ‹‹ዛፍም ትዳር ፈላጊዎችን ያገናኛል›› ሲል አስንብቧል፡፡ ‹‹ብሪድግሮምኦዋክ›› የተሰኘውና በጀርመን አገር የሚገኘው የ500 ዓመት እድሜ ጠገብ ዛፍ ከዚህ ስራው የተነሳ የራሱ የፖስታ አድራሻ የተሰጠውና በየቀኑ 40 የሚሆኑ ደብዳቤዎችን የሚቀበል ነው፡፡ ከመላው አለም ፍቅርን ፈልገው ወደ ጀርመን የሚመጡ ዜጎች ምናልባትም ደብዳቤውን ያገኘው ሰው አንብቦ ዳግም ምላሽ ይሰጠኛል በሚል ተስፋ ደብዳቤያቸውን በዚሁ ዛፍ ቀዳዳ ውስጥ ያስቀምጣሉ፡፡
ይህንንም ተከትሎ ዛፉ ከመላው አለም ወደ ጀርመን ለሚመጡና የፍቅር አጣማጅ ፈላጊዎች ሁነኛ የመገናኛ መንገድ ቢሆንም፤ ከትክክለኛ የፍቅር ተጣማጆች ጋር እኩል ሊወዳደር አይችልም ሲል ዘገባው ይገልፃል፡፡ ይሁን እንጂ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንደ አሸን በፈላበት በዚህ ወቅት ‹‹ብሪድግሮ ምኦዋክ›› የተሰኘው ዛፍ የፍቅር ተጣማጆችን በማገናኘት ረገድ ተወዳጅና ተመራጭ ሆኗል፡፡
‹‹ሰዎች በማህበራዊ ድረ ገፆች አማካኝነት ከሚያደርጉት የትዳር ፍለጋ ግንኙነት በተሻለ ዛፉ አስማታዊ የፍቅር ምትሃት ያለውና መልካም እድልም ይዞ የሚመጣ ነው›› ሲል የ72 ዓመቱ የቀድሞ ፖስተኛ ለቢቢሲ ተናግሯል፡፡
ዝነኛው የፍቅር አጣማጅ ዛፍ ለ500 ዓመታት በምድር ላይ የቆየ ቢሆንም፤ የትዳር አጣማጅ ለመሆን የበቃው ግን ከ100 ዓመት በፊት ታሪካዊ የፍቅር ክስተት ከተፈጠረ በኋላ ነው ሲል ዘገባው ጠቅሷል፡፡
በ1890 ሚና የተሰኘችው የአካባቢው ነዋሪ ዊልሄልም በተሰኘው ቼኮሌት ሰሪ ወጣት ፍቅር ትወድቃለች፡፡ የሁለቱን ፍቅር ግንኙነትን ቀድሞውንም ያልወደዱት አባቷ ግን ልጁን በፍፁም እንዳታገኘው ይከለክሏታል፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱ ፍቅረኛሞች በድብቅ የፍቅር ደብዳቤዎችን በአሁኑ ወቅት የ500 ዓመት እድሜ ጠገብ በሆነውና ‹‹ብሪድግሮምኦዋክ›› በተሰኘው ዛፍ ቀዳዳ አማካኝነት መለዋወ ጣቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ነገር ግን ከአንድ አመት በኋላ የልጅቷ አባት ይህን ድብቅ ግንኙነት ይደርሱበታል፡፡ አባትየው ወደቅጣት ርምጃ ከመሄድ ይልቅ ሁለቱ ፍቅረኛሞች እንዲጋቡም ይሁንታቸውን ይገልፃሉ፡፡ ሁለቱ ፍቅረኛሞችም በችግራቸው ጊዜ እንደመገናኛ ድልድይ ሆኖ ባገለገላቸው ዛፍ ስር ጋብቻቸውን ይፈፅማሉ፡፡
የሁለቱ ጥንዶች ታሪክ ኢውቲን በተሰኘው ቦታና በአካባቢው በመሰራጨቱ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሰዎች ዛፉን በመጠቀም የፍቅር አጋራቸውን ለማግኘት የፍቅር ደብዳቤዎችን በመፃፍ በዛፉ ቀዳዳ ውስጥ በማስቀመጥ መጠቀም ጀምረዋል፡፡ በ1927 ዛፉ ‹‹ብሪድግሮምኦዋክ›› በሚል ስያሜውን ማግኘት እንደቻለና የጀርመን ፖስታ አገልግሎትም ከጀርመንና ከመላው አለም የሚመጡ ሰዎች እንዲጠቀሙ የፖስታ አድራሻና ኮድ አዘጋጅቶለታል፡፡
ይህን ዛፍ የሚጎበኙ ፍቅር ፈላጊዎችም እንደ ቀላል ደንብ እንዲያከብሩ ይደረጋል፡፡ ይኸውም በዛፉ ቀዳዳ ውስጥ ያሉትን ሁሉንም ደብዳቤዎች ማረጋገጥ የሚችሉ ቢሆንም፤ መልስ ሊሰጡበት የሚፈልጉትን ደብዳቤ ብቻ መርጠው ከወሰዱ በኋላ የተቀሩት በቦታው መመለስ ይኖርባቸዋል ሲል ዘገባው ያጠናቅቃል፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

Published in መዝናኛ

የፅንስና ማህፀን ቀዶ ሕክምና በዋናነት ሴቶች ከመራቢያ አካላቸውና ከተዋልዶ ጤና ጋር በተያያዘ የሚያጋጥማቸውን ችግሮች ለማስተካከልና ወደ ጤናማ ሥርዓት ለመመለስ የሚደረግ ሕክምና ነው፡፡
ከኢትዮጵያ የፅንስና ማህፀን ሐኪሞች ማህበር የተገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ በኢትዮጵያ የማህፀንና ፅንስ ሐኪሞች ቁጥር 350 ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ሕክምናውን ከሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ጋር ሲነፃፀር አሁንም ዝቅተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡ ባለፉት አስርና አስራ አምስት ዓመታት በፅንስና ማህፀን ሕክምና የድህረ ምረቃ ትምህርት የሚሰጥባቸው ተቋማትም በቁጥር አነስተኛ ነበሩ፡፡
በአሁኑ ወቅት ትምህርቱን የሚሰጡ ተቋማት ቁጥራቸው ወደ 12 ማደጉን ተከትሎ በርካታ ባለሙያዎች ሥልጠና እያገኙ ነው፡፡ አገሪቷ ውስጥ ባሉ ቁጥራቸው 50 በሚደርስ የግልና የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የቅድመ ምረቃ ትምህርት በመጀመሩም በቀጣይ በተከታታይ የስፔሻሊቲ ሥልጠና ይሰጣል፡፡ ይህም በአሁኑ ወቅት የሚስተዋለውን የዘርፉ ሕክምና የባለሙያዎችን እጥረት የሚያቃልል እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ በቅርቡም የኢትዮጵያ የፅንስና ማህፀን ሐኪሞች ማህበር ባደረገው 26ኛ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ጥራቱና ደህንነቱ የተረጋገጠ የማህፀንና ፅንስ ሕክምና ተደራሽነትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል፡፡
የማህፀንና ፅንስ ሕክምና ባለሙያዋ ናርዶስ ተመስገን የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ኮሌጅ ባመቻቸላት የትምህርት ዕድል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊቲ ፕሮግራም የድህረ ምረቃ ትምህርቷን ተከታትላ አጠናቃለች፡፡ ተደራሽ የሆነ የማህፀንና ፅንስ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ችግሮች በአገሪቷ መኖሩንም ገልፃ፤ በተለይ በዘርፉ ሠልጥነው የሚመረቁ ባለሙያዎች ችግሩን ከማቃለል አኳያ የራሳቸውን አስተዋፅኦ ያበረክታሉ፡፡ የቀሰሙትን ትምህርትም ከበታች ላሉ ባለሙያዎች ለማስተላለፍም ሁነኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ በማህፀንና ፅንስ ሐኪሞች ማህበር በኩልም የሚደረገው ትብብርና ድጋፍም ሕክምና አገልግሎቱን በጥራት ለማዳረስ ያግዛል፡፡
ባለሙያዋ እንደምትለው ከሆነ፤ የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊቲ ፕሮግራም ትምህርቷን ስትከታተል ማህበሩ ሙያ ነክ እንዲሁም የማቴሪያልና የመፅሐፍት ድጋፎችን አድርጓል፡፡ የማህበሩ አባል በመሆኗና ማህበሩ ከሚያቀርባቸው የምርምርና ጥናት ሥራዎች የተለያዩ ልምዶችን አግኝታለች፡፡ ይህም በቀጣይ በሙያዋ ለምትሰጠው የሕክምና አገልግሎት ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡
ዶክተር ኤልናታል አዲሴ በተመሳሳይ ከሚሠራበት የሃዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ባመቻቸለት የትምህርት ዕድል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊቲ ፕሮግራም የድህረ ምረቃ ትምህርቱን ተከታትሎ አጠናቋል፡፡ በኢትዮጵያ ጥራቱና ደህንነቱ የተጠበቀ የማህፀንና ፅንስ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ ውስንነቶች እንዳለ ገልፆ፤ ይህን ለማሻሻል እነ እርሱን ጨምሮ በዘርፉ ትምህርታቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁ ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ የፅንስና ማህፀን ቀዶ ሕክምና የቡድን ሥራ ከመሆኑም አኳያ በሕክምናው የሚታየውን የባለሙያዎች እጥረት ለጊዜውም ቢሆን ከማቃለል አንፃር የበኩሉን አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡
እንደ ዶክተር ኤልናታል አባባል፤ በማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊቲ ፕሮግራም ትምህርት በነበረው የአራት ዓመት ቆይታ ቀዶ ሕክምናውን በመሪነት ለማከናወን የሚያግዘውን ልምድና እውቀት ማግኘት ችሏል፡፡ የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት ሐኪም በአገሪቷ ውስን ከመሆኑ አኳያ አሁንም የተደራሽነት ችግሮች ቢኖርም፤ እርሱን ጨምሮ በጊዜው ተከታታይ ትምህርት እየተሰጠ በመሆኑ አሁን ላይ ያለውን ችግር በመጠኑም ቢሆን ያቃልለዋል፡፡ በቀዶ ሕክምናው ላይ በቶሎ ውሳኔ መስጠትም ዋናው ጉዳይ መሆኑንም ጠቅሶ፤ ከዚህ አኳያ እርሱን መሰል በዘርፉ የሚሠለጥኑ ባለሙያዎች ቁጥር ከፍ ካላለ ታካሚዎች ላይ የራሱ አሉታዊ ተፅእኖ ያሳድራል፡፡
የኢትዮጵያ ፅንስና ማህፀን ሐኪሞች ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ደረጀ ንጉሴ እንደሚገልፁት፤ በኢትዮጵያ ጥራቱና ደህንነቱ የተጠበቀ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ለተገልጋዮች ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ውስንነቶች አሉ፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች በማደግ ላይ ባሉ አገራት ላይም የሚስተዋል ችግር ነው፡፡ አገልግሎቱም ቢሆን በዋና ዋና ከተሞች ላይ ብቻ ተወስኖ የሚሰጥ ነው፡፡ ተደራሽነቱን ከማስፋትና ጎን ለጎን ጥራቱን የጠበቀ የፅንስና ማህፀን ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ለሕሙማን ለማዳረስ ጊዜው አሁን ነው፡፡ ከዘላቂ የልማት ግቦች ውስጥ አንዱ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠውም ይገባል፡፡
እንደ ዶክተር ደረጀ ገለፃ፤ ጥራት ያለውና ደህንቱ የተረጋገጠ የፅንስና ማህፀን ሕክምና አገልግሎትን በአገሪቱ ተደራሽ ለማድረግ ለፅንስና ማህፀን ሐኪሞች ማህበር አባላት ተከታታይነት ያለው ትምህርትና ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይም ይህንኑ አገልግሎት ለሚሠጡ የጤና ተቋማት ማህበሩ ሥልጠናዎችን በማመቻቸት ይሰጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሙያው ሠልጥነው ለሚመረቁ አዳዲስ ሐኪሞች በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በመድረስ አገልግሎቱን ተደራሽ እንዲያደርጉ አስፈላጊውን ድጋፍ ማህበሩ ያደርጋል፡፡
በግል ጤናው ሴክተርና በመንግሥት የጤና ተቋማት ውስጥ የሚታዩ በቀዶ ሕክምና የማዋለድ ቁጥሮች የመጨመር ምክንያቶችን ነቅሶ ማውጣት አስፈላጊ መሆኑን የሚጠቅሱት ዶክተር ደረጀ፣ ይህን ተቀራራቢ ለማድረግና የማህፀንና ፅንስ ቀዶ ሕክምና አገልግሎቱን ለሕሙማን ተደራሽ ለማድረግ ጠንካራ ሥራ መሠራት እንደሚገባም ያመለክታሉ፡፡ የማህፀንና ፅንስ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ለሕሙማን በሚሰጡበት ጊዜ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ወይም ውስብስብ ጉዳዮችን ለመቀነስ የችግሮቹን አይነት በመለየት መፍትሄ መስጠት እንደሚያስፈልግም ነው የሚናገሩት፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም በመካከለኛ ደረጃ የጽንስና ማህፀን ሕክምና የሚሠለጥኑ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችን ቁጥር ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከበደ ወርቁ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ በጤናው ዘርፍ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ከተቀመጡት አራት የትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎች ውስጥ አንዱ ጥራትና ተደራሽነት ነው፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም አስፈላጊና አስቸኳይ የቀዶ ሕክምና ቁልፍ ሚና እንዳለው በመገንዘብ ‹‹ ደህንነቱን በጠበቀ የቀዶ ሕክምና ህይወትን ማዳን›› የሚል ኢኒሺዬቲቭ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ፤ በኢትዮጵያ በተለይም የፅንስና ማህፀን አስቸኳይ የቀዶ ሕክምና ተደራሽነት ውስንነቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህን ለማሻሻል በሚኒሰቴር መሥሪያ ቤቱ እየተተገበሩ ያሉትን ሥራዎች ለማገዝ የኢትዮጵያ ፅንስና ማህፀን ሐኪሞች ማህበር ሙያዊ አስተዋፅኦ ሊያድርግ ይገባል፡፡ ማህበሩ ለአባላቱ በየወቅቱ በዘርፉ የሚመጡ አዳዲስ ሳይንሳዊ ግኝቶችን ለማሳወቅ የሚያደርገው ጥረት ጥራቱና ደህንነቱ የተጠበቀ የፅንስና ማህፀን ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ወሳኝ ድርሻ ስለሚኖረው ይህን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

Published in ማህበራዊ

ከቅርብ ጊዜያት ጀምሮ ኢትዮጵያን የሚፈታተናት የሰላም እጦት አንዴ ጋብ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ አየል ሲል መቆየቱ ይታወቃል፡፡ በተደጋጋሚም በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ሕገ ወጥ ተግባራት በመፈጸማቸውም በርካታ ሰዎች ህይወታቸው ጠፍቷል፤ ለከባድ የአካል ጉዳትም ተዳርገዋል፡፡ በተጨማሪም የልማትና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከመዳከሙም በላይ ህገ መንግሥቱም አደጋ ላይ ወድቋል፡፡

የሰላም መደፍረሱንና ልማት መስተጓጎሉን ወደቀድሞው ለመመለስ በመንግሥት በኩል አንዳንድ ጥረቶች ቢደረጉም፤ ምላሹ ግን አዎንታዊ መሆን አልቻለም፡፡ መንግሥትም በመደበኛው የህግ ማስከበር ሥርዓት ለመከላከልና ለመቆጣጠርም ከአቅሙ በላይ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም ህገ መንግሥቱ ባስቀመጠው የህግ ሥርዓት መሰረት የተወሰኑ መብቶችን በመገደብ ሰላምንና ልማቱን ለማስቀጠል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መውጣቱ እሙን ነው፡፡
የኢፌዴሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም ‹‹ህገ መንግሥቱንና እና ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል›› በሚል ያወጣውን ይህንኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከሰሞኑን የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ በመወያየት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ ደግፎ ማጽደቁ ይታወቃል፡፡ በዕለቱም ከተገኙት 490 አባላት ውስጥ ለአዋጁ ድጋፍ የሰጡት 395ቱ አባላት ሲሆኑ፣ 88ቱ የተቃወሙ እንዲሁም ሰባት አባላት ደግሞ ድምጻቸውን ያቀቡ ናቸው፡፡
በዕለቱ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬ ለአባላቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስፈላጊነት አስመልክተው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ህገ መንግሥቱና ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለአደጋ የሚያጋልጡ ተግባራትና ዝንባሌዎች በስፋት እየተስተዋሉ መጥተዋል፡፡ በዚህም የህዝብና የአገር ሰላምና ጸጥታ በመታወክ ላይ ይገኛል፡፡ ዜጎችም በሰላም ወጥተው በሰላም ለመግባት ባለመቻላቸው ስጋት ውስጥ ወድቀዋል፡፡ የህዝቦች በአንድነት የመኖር እሴትም በመሸርሸር ላይ ይገኛል፡፡
በዚህም የሰው ህይወት ከመቀጠፉም በተጨማሪ ብሔርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ተፈጽመዋል፡፡ ህዝቦች ተፈናቅለዋል፡፡ የዜጎችም በነጻነት የመዘዋወርና በመረጡት ቦታ በመኖር ሀብት የማፍራት መብታቸው ተጥሷል፡፡ እንዲህ አይነቱን ህገ ወጥ ድርጊት ለመከላከልና የህዝቡን ሰላም ለማስጠበቅ እንዲሁም ልማቱም እንዳይስተጓጎል ለማድረግ ሲባል አዋጁ ሊወጣ መቻሉን ነው ዓቃቤ ህጉ ያስረዱት፡፡
ይሁንና በዕለቱ ጥቂት ከማይባሉ የምክር ቤቱ አባላት ‹‹አዋጁ ግልጽነት የጎደለው ነው፤ መስተካከል የሚገባቸው ሐሳቦች አሉት፡፡ አሻሚ ጉዳዮችን ይዟል›› የሚሉና መሰል አስተያየቶች እንዲሁም የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ በተለይም በአዋጁ ክፍል ሁለት፣ አንቀጽ አራት፣ ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ ‹‹ማንኛውም ሁከት፣ ብጥብጥና በህዝቦች መካከል መጠራጠርና መቃቃር የሚፈጥር ይፋዊ የሆነ የድብቅ ቅስቀሳ ማድረግን…ይከለክላል›› በሚለው ሐሳብ ውስጥ ‹‹ይፋዊ የሆነ የድብቅ ቅስቀሳ ማድረግ›› የሚለው ሐሳብ በራሱ የሚጣረስ ሆኖ እንዳገኙትም ነው የምክር ቤቱ አባላት የተናገሩት፡፡
አባላቱ፣ ክፍል ሁለት፣ አንቀጽ አራት፣ ንዑስ አንቀጽ ሰባት ላይ የቀረበው ‹‹የሰዓት እላፊ ተፈጻሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ይወስናል፤ ለተወሰነ ጊዜ አንድን መንገድ፣ አገልግሎት መስጫ ተቋም እንዲሁም ሰዎች ለጊዜው በተወሰነ ቦታ እንዲቆዩ፣ ወደተወሰነ አካባቢ እንዳይገቡ ወይም ከተወሰነ ቦታ እንዲለቁ ያዛል›› የሚለው ሐሳብና አስራ ሁለተኛው ንዑስ አንቀጽ ላይ ደግሞ ‹‹ህዝብ የሚገለገልባቸው የአገልግሎት ተቋማት፣ የንግድ ሥራዎች ወይም የመንግሥት ተቋማት ከሚሰጡት አገልግሎት እንዳይስተጓጎሉ ተገቢው ጥበቃ ይደረጋል፤ ይህን ተላልፎ አገልግሎቱን ያቋረጠ ማንኛውም ሰው በህግ ተጠያቂ ይሆናል›› በሚል የሰፈረው ሐሳብ የሚጋጭ ነው በማለት አስተያየታቸውን በስጋት ሰንዝረዋል፡፡
አንዳንዶች ደግሞ ምንም እንኳን የአዋጁን መጽደቅ ባይቃወሙም ‹‹አዋጁ አገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀብላ ያጸደቀቻቸውን ኮንቬንሽኖች የሚጻረር ነው›› በማለት ስጋታቸውን ሲገልጹ፣ ሌሎች ደግሞ ክፍል ሁለት፣ አንቀጽ አራት፣ ንዑስ አንቀጽ 15 ላይ ያለውን ‹‹ህገ ወጥ የመሬት ወረራን፣ ህገ ወጥ ግንባታን፣ ኢንቨስተሮችን ማፈናቀልን የሚሠሩበትን ቦታ ከህግ ውጪ የመውሰድ ድርጊቶችን ይከለክላል›› የሚለውን ሐሳብ በመቃወም ‹‹አዋጁ ከመሬት ወረራ ጋር ምን አገናኘው›› ሲሉ ሞግተዋል፡፡ እንዲሁም ‹‹አዋጁ፣ ሲሆን ሲሆን የጸጥታና ሰላም ጉዳይ ላይ ማጠንጠን ሲገባው የአገሪቱ ሀብትና ኃይል ላይ መንጠልጠሉስ ለምን አስፈለገ›› በማለትም ጠይቀዋል፡፡ ‹‹በአካባቢያችን ምንም የተፈጠረ ችግር በሌለበት አዋጅ ማወጁ ተገቢ አይደለም›› የሚሉና ችግር እንኳ ቢፈጠር ከተፈጠረበት አካባቢ አቅም በላይ ባለመሆኑ የሚስተካከል ስለመሆኑ የተናገሩ አባላት አልታጡም፡፡ የተወሰኑት ደግሞ አዋጁ ከመጽደቁ በፊት እንደገና ውይይት እንዲደረግበትም አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
በአንጻሩ ደግሞ አብዛኛዎቹ የምክር ቤት አባላት የአዋጁን አስፈላጊነትና መጽደቅ ደግፈው ሐሳባቸውን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ምክንያታቸው ደግሞ በቅድሚያ የህዝብን ሰላም ማረጋገጥ ተገቢ ጉዳይ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ ‹‹ይጋጫሉ›› ተብለው በሌሎቹ አባላት የተነሱትንም ንዑሳን አንቀጾች የሚጋጭ መስሎ እንዳልታያቸወም ነው ያስረዱት፡፡ አዋጁ የግድ እያንዳንዱን ጉዳይ ዘርዝሮ ማስቀመጥ አለበት የሚል እምነትም እንደሌላቸው በአስተያየታቸው ወቅት ተናግረዋል፡፡ የአዋጁ ዋና ዓላማ የህዝብን ሰላም ማረጋገጥ እስከሆነ ድረስም የህዝብን ሰላም የሚፈልግ አካል ሊቃወመው እንደማይገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡
በዕለቱ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ጌታቸው እንደተናገሩት፤ የአዋጁ አስፈላጊነት ላይ ገዢ ሆኖ መታየት ያለበት ጉዳይ፣ በኃይል የታገዘ ሁከትና ብጥብጥ ለማጥፋት መሆኑ ነው፡፡ የነገሠውን ሥርዓት አልበኝነትንም ማስቀረትና ሰላምን ማረጋገጥ ተገቢ በመሆኑ በአዋጁ አስፈላጊነት ላይ ግርታ መፈጠር የለበትም፡፡ ክፍል ሁለት ላይ አንቀጽ አራት ንዑስ አንቀጽ አንድ የሚያምታታ ሐሳብ ነው ተብሎ የተቀመጠው ዞሮ ዞሮ ማንኛውንም ሁከትና ብጥብጥ ለመከላከል የተቀመጠ እንጂ ሌላ ዓላማ የለውም፡፡ በይፋም ሆነ በድብቅ የሚከናወን ሁከትም ሆነ ብጥብጥ መቼም ቢሆን ሰላም የማይሰጥ ስለመሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ዋናው ዓላማ የህዝብን ሰላም ማስፈን ነው፡፡
ንዑስ አንቀጽ ሰባት ላይና ንዑስ አንቀጽ 12 ላይ የተቀመጠው ሐሳብ እንደማይጣረስ የሚያስረዱት ዓቃቤ ህጉ ጌታቸው፣ ‹‹አንቀጽ ሰባት ላይ የተቀመጠው ሐሳብ ከሰዓት እላፊ ጋር ተያይዞ ሊዘጉ የሚችሉ የአገልግሎት ተቋማት አሉ ተብሎ ከታመነ በዚህ ሰዓት ሊዘጉ ይችላሉ ብሎ ኮማንድ ፖስቱ ሊያስቀምጥና ሊመልስ እንደሚችል ነው የሚያስበው›› ሲሉ ነው ያብራሩት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ንዑስ አንቀጽ 12 ግን የብጥብጥና የሁከት ወኪል እና ኃይል በሆነው አካል ፍላጎትና ግፊት የአገልግሎት ተቋማት በምንም መንገድ ሊዘጉ አይችሉም፤ እንዳይዘጉ መከላከል መቻል አለበት የሚል በመሆኑ ሁለቱ ሃሳቦች እንደተባለው የሚለያዩ አይደሉም በማለት ነው የገለጹት፡፡ የሁለቱም ሐሳብ ይዘት የህዝብን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ እንደሆነም ነው ያመለከቱት፡፡ በዚህም እይታን እንጂ በምንም መልኩ ስጋት አይሆንም በማለትም ያመለክታሉ፡፡
በዚሁ ክፍልና አንቀጽ፣ ንዑስ አንቀጽ 15 ላይ በተቀመጠው ሐሳብ ከአባላቱ ተደጋግሞ የተነሳው የ‹‹መሬትና ሰላም ምን አገናኘው›› ጥያቄ ጠቅላይ ዓቃቤ ህጉ ሲመልሱ እንዳሉት፤ ሥራው የፌዴራልም የክልልም ቢሆንም ይህንኑ ሥራ በተለመደው የህግ ማስከበር አግባብ ሊፈጽም የቻለ የፌዴራልና የክልል መንግሥት ባለመኖሩ የተነሳ ነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያስቀመጠው፡፡ እንዲያውም አሁን አሁን የሚታየው ጉዳይ ህግና ሥርዓት የለም በሚያስብል አይነት ነው መሬት በይፋ እየተወረረ ያለው፡፡ በህገ ወጥ መንገድም በይፋ ቤት በመገንባት ላይ መሆኑን ተደርሶበታል፡፡ ይህ ሁሉ ህግ ባለበት አገር እየተከናወነ በመሆኑም የህግ የበላይነት መስፈን ይጠይቃልና ጉዳዩን በህግ ማቆም ያስፈልጋል፡፡ መሬት ደግሞ የአገሪቱ ውስን ሀብት እንደመሆኑ ዘላቂና የላቀ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ሊሰጥ በሚችል መንገድ ነው መመራት ያለበት እንጂ በዘፈቀደ መሆን የለበትምና ህገ ወጥ ግንባታ ሊቆም የሚገባው እንቅስቃሴ ነው፡፡
እርሳቸው እንዳሉት፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዋና ዓላማ አገሪቱ ለተያያዘችው ዋነኛ አጀንዳ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ነው፡፡ በዚህ ውስጥ የልማት፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን በተሳካ መንገድ እንዲጓዙ ማድረግም ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ለማሳካት ኃላፊነት የሚሰማው አካል ሊኖር ይገባል፡፡
በዕለቱ አዋጁ ከጸደቀ በኋላ ላነጋግራቸው ፈቃዳቸውን ከጠየቅኳቸው የምክር ቤት አባላት መካከል ብዙዎቹ እሽታቸውን ነፍገውኛል፡፡ ለእንቢታቸው ምክንያቱ ምን እንደሆነ እንዲያጋሩኝ ባግባባቸውም ሊነግሩኝ አልወደዱም፡፡
ይሁንና አስተያየታቸውን ካጋሩኝ የምክር ቤት አባላት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ናስር ካንሶ እንደሚሉት፤ የአዋጁ መጽደቅ ታሪካዊ ነው ተብሎ የሚወሰድ ነው፡፡ በመሆኑም አፎይታን የሚሰጥ ነው፡፡ አዋጁ እንዳይጸድቅ ድምጻቸውን የነፈጉ አባላት ከየአካባቢያቸው ነባራዊ ሁኔታ ተነስተው በመወሰናቸው ትክክለኛ ናቸው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
እንዲያም ሆኖ ግን ይላሉ የምክር ቤቱ አባል አቶ ናስር፣ ይህን አዋጅ የሚቃወመው ትክክለኛው ህዝብ ሳይሆን በወንጀል ላይ የተሳተፉ አካላት ናቸው፡፡ ህዝቡ በየትኛውም መንገድ ቢሆን ማህበራዊ እሴቱን የሚንድበትን ነገር አይፈልግም፤ ዜጋውም ያላግባብ እንዲመታበት አይሻም፡፡ የአብሮነት ባህሉም እንዳይናድ የበኩሉን ጥረት የሚያደርግ ህዝብ ነው፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤ አንዳንድ አካባቢ ዜጎች በራቸው ላይ ቀይ ምልክት እየተደረገ እየተጠቁ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት ባለበት አገር ትክክለኛ አርማ የሆኑ በሌላ ዓርማ ተቀይረው ይታያሉ፡፡ በመደበኛ ሁኔታ ሲታይ መሰረት የሆነው የአገሪቱን ህግ በአግባቡ ለመተግበር አስቸጋሪ ጊዜ ተፈጥሯል፡፡
‹‹ስለዚህም እነዚህን ችግሮች ወደ መደበኛው እንቅስቃሴ ለማምጣት መንግሥት እንደመንግሥት የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የሥራ ዕድል ችግር አለ፤ እነዚህንም እኔ የፈጠርኳቸው ናቸውና እኔው ላስተካክል ብሎ ያስቀመጣቸውን አቅጣጫ ለመፈጸም አስቸጋሪ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ስለሆነ እነዛንም ወደ አፈጻጸም ለማስገባት የህዝቡንም ሰላም ለመጠበቅና የነበረውን የአብሮነትና የመተሳሰብ ባህል ለማስቀጠል ወሳኝ የሆነ አዋጅ ነው›› ይላሉ፡፡
ምንም እንኳ የየአካባቢያቸው ጉዳይ አሳስቧቸው የተቃወሙ የምክር ቤት አባላት ቢኖሩም በሁለት ሦስተኛ ድምጽ ድጋፍ ጸድቋልና ለኢትዮጵያ ህዝብ ታሪካዊ ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡ ድምጻቸውን ያልስጡም ይሁኑ የታቀቡት የሚኮነኑበት ሳይሆን ሁኔታዎች አስገድዷቸው ነውና ያለው ጉዳይ በአግባቡ በመፈተሽ አዋጁን መተግበር ነው የሚጠበቀው ሲሉም ነው ያመለከቱት፡፡
ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ታደለ አሰፋ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ያጸደቁት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያለውን ሰላምና መረጋጋት የማጣት ችግርን የሚያቃልል ነው፡፡ ቀደም ሲል እየተስተዋለ ያለው ጉዳይ ሕዝብ ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ መንቀሳቀስ አልቻለም፡፡ አገሪቱ በብዙ ምልጃ ያመጣቻቸው በሥራ ላይ የሚገኙት ኢንቨስትመንቶች በመውደም ላይ ናቸው፡፡ በዚህም አገሪቱ አደጋ ላይ በመውደቋ ህገ መንግሥት በመደበኛው ህግ መሰረት ማስከበር አልተቻለምና አዋጁ የግድ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
በሌሎች የምክር ቤቱ አባላት አዋጁ ድጋፍ ያለማግኘቱ ምክንያት ምን ይሆን ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄ ‹‹ቀደም ሲል ታውጆ የነበረው አዋጅ በሚተገበርበት ወቅት ችግሮች እንደነበሩበት ወደመረጣቸው አካል በሄዱበት ጊዜ ሰማን በማለትና እነዚህ ችግሮች ደግሞ እንደማይደገሙ ምን ማረጋገጫ አለ የሚል ስጋት ሰላለባቸው ይሆናል›› ሲሉ ነው ምላሸ ለመስጠት የሞከሩት፡፡
አዋጅ ጸድቋልና ከህዝቡ የሚጠበቀው ምንድን ነው ተብሎ ለተነሳው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ፤ ‹‹በየአካባቢው የሚቋቋመውን ኮማንድ ፖስት በመተባበር ለሰላሙ መስፈን የበኩሉን ሚና መጫወት ነው›› በማለት ገልጸዋል፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላስቀመጣቸው ደንቦችና መመሪያዎች ለተፈጻሚነታቸው የበኩላቸውን ሊያደርጉም እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ በአዋጁ የሚከለከሉና የሚፈቀዱትን በጽኑ ማክበር ለሰላም የጎላ ድርሻ አለውና ቢተባበሩ መልካም ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
አቶ ናስር፣ አዋጁ ባይጸድቅስ ኖሮ ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ እንደተናገሩ፤ ለአገሪቱ ሰላም መጠበቅ ለሚደረገው እንቅስቃሴ ከባድ ነበር የሚሆነው፡፡ አሁን ላይ በአንዳንድ አካባቢዎች ወጣቶች ተደራጅተው የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የአካባቢው ህዝብ በጥንቃቄና በትዕግስት እያየው ነው ያለው፡፡ ከራሳቸው ችግር ተነስተው የሚያደርጉት ከሆነ ለችግሮቻቸው መንግሥት ምላሽ ሲሰጥ ያቆማል የሚል እምነት አለ፡፡ የማፈንገጥም ነገር ካለ የሚታወቅ ነው የሚሆነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ሁኔታው የሥርዓት ለውጥ መፈለግ ከሆነ፣ ሥርዓትን ማስተካከልና ለውጥ እንዲመጣ የሚደረገው አካሄድ በጉልበት በመናድ ሳይሆን በአግባቡ በመጠየቅ ሊሆን የሚገባ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ይህንን ሁሉ ለማድረግ ግን በመጀመሪያ ለሥርዓቱ ተገዢ መሆኑን ይጠይቃል፤ ነገር ግን ይህ ሥርዓት በመጥፋቱ ወደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተመጥቷል፡፡ አዋጅ ደግሞ ባይጸድቅ ኖሮ የከፋ ችግር ይፈጠራል በማለት ነው አስተያየታቸውን ያጋሩኝ፡፡
አዋጅ ያልጸደቀ ቢሆን ኖሮ ኢ-ፍትሃዊነት እየነገሠ ይሄዳል፡ ህግ በመጣሱ በአንዳንድ አካባቢዎች በደል እየደረሰበት ያለ የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ ትዕግስቱ ሲሟጠጥ ራሱን ወደ መከላከል አቋም ውስጥ መገባቱ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ የሚወስደው አገር ወደ መፍረስና ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ነው፡፡ እስካሁን በሚታየው እንኳ መታዘብ የሚችል አካል ካለ የመንግሥት ተቋማት እንዲሁም ማረሚያ ቤቶች እየፈረሱ ናቸው፡፡ በዚህ ውስጥ ደግሞ ሰው ሰውን ይገድላል፤ የሚጠየቅበት የፍትህ ተቋም ደግሞ አይኖርምና ለአገር መፈራረስ ትልቁን ሚና ይጫወታል›› ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡
 

Published in ፖለቲካ

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2025 በአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ቀዳሚ ማዕከል የመሆን ርዕይዋን እውን ለማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ፣ በዘርፍ የተለየ፣ ዘላቂ ፣ የእሴት ሰንሰለት ያለውና በኤክስፖርት ተወዳዳሪነት ላይ ያተኮረ የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ቁልፉን ሚና ይጫወታል። በአገሪቱ የኢንዱስትሪ ልማት ውስጥ የአዳማና የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታቸው እየተጠናቀቀ እንደሚገኝ መንግሥት ሲገልፅ፤ የኮምቦልቻና መቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ የቦሌን ለሚንና ሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመከተል ማምረት ለመጀመር የተለያዩ ቅድመ-ምርት ተግባራትን እያከናወኑ ይገኛል።
የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኩ መስከረም 2009 ዓ.ም የሳይት ርክክብ ተደርጎ በይፋ ግንባታ ተጀምሮ በዘጠኝ ወር ውስጥ ተጠናቆ ባለፈው ዓመት መጨረሻ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደተመረቀ የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ኮርፖሬሽን የኦፕሬሽንና ማኔጅመንት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ሰለሞን ይናገራሉ።
ኢንዱስትሪ ፓርኩ ከተመረቀ በኋላ በዋናነት ትኩረት ተሰጥቶ ሲሠራ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር የመዘርጋት እና የማገናኘት፣ በኢትዮ ቴሌኮም አማካይነት የቴሌኮሙኒኬሽን መሰረተ ልማት ቀሪ ሥራዎች የማጠናቀቅ፤ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ከዋና የከተማዋ መንገድ ጋር የማገናኘት እንዲሁም የፍሳሽ ማጣሪያ ተቋም ግንባታ የማፋጠን ሥራዎች ላይ እንደነበር ማብራሪያ የሚሰጡት አቶ ሽፈራው፤ በሌላ በኩል ከምረቃ በኋላ ከኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን ለሠራተኞች የመኖሪያ ቤት አቅርቦት፣ የሠራተኛ አቅርቦት፤ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ጸጥታና ደህንነት ጋር የተያያዙ ሥራዎች በጋራ እየተሠሩ እንደሚገኙም ይገልጻሉ።
በተለይም ለኢንዱስትሪ ፓርኩ ልማት ሲባል ከቦታው የተነሱ የህብረተሰብ ክፍሎች በኢንዱስትሪ ፓርኩ የተለያዩ ተግባራት ላይ የሚሳተፉበት እና በቀጣይነት ባለው መልኩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚረዱ ተግባራት ተለይተው እየተሠሩ እንደሆነም ይናገራሉ።
በመጀመሪያው ምእራፍ በ75 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ፤ ዘጠኝ የተለያዩ ስፋት ያላቸው የፋብሪካ ሼዶችን፣ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ጎን ለጎን አራት የፋብሪካ ሼዶችን ሊያስገነባ የሚችልና አስፈላጊ መሰረተ ልማት ተሟልቶለት የተዘጋጀ ሲሆን፣ ባለሀብቶች በስታንዳርዱ መሰረት ለመገንባት ሲፈልጉ ዝግጁ የሆነ የለማ መሬትም እንዳለም ነው ያመለከቱት፡፡
አቶ ሽፈራው፣ በፓርኩ ከገቡ ባለሀብቶች አንዳንዶቹ ወደ ምርት ተግባር በመግባት ላይ ሲሆኑ፤ ቀሪዎቹ የሠራተኛ ምልመላና ሥልጠና እንዲሁም የማሽን ተከላ ሥራ ላይ እያከናወኑ እንደሚገኙም ነው የሚያስረዱት።
ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው እንደሚሉት፤ የኢንዱስትሪ ፓርኩ የአልባሳት ምርት ለማምረት ከሚውሉ ሼዶች ግንባታ በተጨማሪ የራሱ የእሳት አደጋ መከላከያ ተቋም ያለው ሲሆን፣ ለዚሁ ተግባር በአዲስ አበባ ከተማ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ሥልጠና እየተሰጣቸው ባሉ ባለሙያዎች የተደራጀ ነው። ለኢንዱስትሪ ፓርኩ ሠራተኞች አገልግሎት የሚሰጥ ክሊኒክም ተገንብቷል። የኢንዱስትሪ ፓርኩን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ እንዲረዳ የራሱ የፖሊስ ጣቢያ ህንጻ ይዟል። በኢንዱስትሪ ፓርኩ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከተቆፈሩ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች የሚወጣ ውሃ በአግባቡ ተጣርቶ ለአገልግሎት የሚቀርብበት ተቋም፣ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ቴሌኮም፣ መንገድ የተሟላለት እና አረንጓዴ ልማትም የተከናወነበት ነው።
ለባለሀብቶቹ በአንድ መስኮት መንግሥታዊ አገልግሎቶችን አካቶ የያዘ ባንክንና ጉምሩክን ጨምሮ የተካተቱበት የአንድ ማእከል አገልግሎት መስጫ ተደራጅቶላቸዋል። በሌላ በኩል ከኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚወጣው ፍሳሽ በአግባቡ የሚያዝበትና የሚጣራበት ተቋም እየተገነባለት ይገኛል። በአጠቃላይ መንግሥት 81 ነጥብ 6 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ እያወጣበት ያለ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሲሆን፣ በቀጣዮቹ ዓመታትም የባለሀብቶች ፍልጎትን መሰረት በማድረግ የማስፋፋት ሥራም ይከናወንለታል።
ኮርፖሬሽኑ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እና በኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ላይ ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው ከፍተኛ የሰው ኃይል የሚሳተፍባቸው እና የወጪ ምርቶች ላይ የሚያተኩሩ ዘርፎችን ሊያስተናግዱ የሚችሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በመጀመሪያው ምእራፍ ለመገንባት በያዘው እቅድ መነሻነት በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአልባሳት ምርት የሚያመርቱ ባለሀብቶች የሚሳተፉበት ኢንዱስትሪ ፓርክ ለማዘጋጀት ጥረት አድርጓል፡፡ ስለሆነም ኢንዱስትሪ ፓርኩ በዋናነት በአልባሳት ምርቶች ላይ ትኩረት አድርገው ለሚሠሩ ባለሀብቶች የተዘጋጀና በዚሁ አግባብ ለባለሀብቶች በኪራይ በመተላለፍ ላይም ነው።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆንም፣ ከሌሎች አገራት ተሞክሮ በመነሳት የልማቱም ሆነ የኦፕሬሽንና ማኔጅመንት ሥራው ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ አቅሙን በማጎልበት ላይ ይገኛል፡፡ ስለሆነም የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክም ሆነ ሌሎች ወደ ሥራ የሚገቡ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን የማስተዳደር ሥራው በዋናነት የሚከናወነው በኮርፖሬሽኑ ሲሆን፣ ኮርፖሬሽኑ አስፈላጊ ነው ብሎ ባመነበት ጊዜ በማኔጅመንት ኮንትራት ለሦስተኛ ወገን የማስተዳደሩን ሥራ ሊሰጥ የሚችልበት አግባብም ዝግ አይደለም፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ምክትል ኮሚሽነር ዶክተር በላቸው መኩሪያ የማምረቻ ሼዶቹን በባለሀብቶች ቀድመው እንዲያዙ መደረጉንና ዘጠኙ የፓርኩ የፋብሪካ ህንፃ ወይም ሼዶች በባለሀብቶች መያዛቸውን ይጠቁማሉ።
ልክ እንደ ሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በኮምቦልቻም ስም ያላቸው ኩባንያዎች ተመርጠው መግባታቸውን ያስታወሱት ዶክተር በላቸው፣ ከእነዚህ መካከል የደቡብ ኮሪያው ቱን ኮክና የኢጣሊያኑ ኢካርቢኮ፣ የቻይናው ሳይ ቴክስና የአሜሪካው ትራይብስ ኩባንያዎች የሚጠቀሱ ናቸው ይላሉ።
ኩባንያው ከ40 ዓመት በላይ ልምድ ያለው፣ በቬትናም ባለው ኢንቨስትመንት 20 ሺ ሠራተኞችን በሥሩ የያዘና ዓለም አቀፍ ታዋቂነትን የገነባ ኩባንያ መሆኑንም ይናገራሉ። ኩባንያው አሥር ሺ የሚሆነውን የሥራ ዕድሉን ወደ ኢትዮጵያ ይዞ ለመምጣት በማሰብ በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ አራት የሚያህሉ የፋብሪካ ህንፃዎች በመውሰድ ሥራ ጀምሯል። ኩባንያው ከቆዳና ከሴንቴቲክ ምርቶች የሚሠሩ ቦርሳዎችን በማምረት ይታወቃል ያሉት ዶክተር በላቸው፤ እንደ ቶሚ፣ ኮች፣ ማይክል ኮርስ የተባሉ ትልልቅ ብራንዶች የሚያመርት መሆኑን ነው የሚያስረዱት።
እንደ ዶክተር በላቸው አነጋገር፤ ኩባንያው ማሽኖችን በማስገጠም እና ሠራተኞችን በማሠልጠን ሥራ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ሃምሳ ኢትዮጵያውያን አስፈላጊ የምርት ክህሎት እንዲያገኙ ወደ ቬትናም አቅንተው እየሠለጠኑ ይገኛሉ። የሠራተኞች መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ከመንግሥት መሬት በመረከብ ሥራ ጀምረዋል።
የኢጣሊያኑ ኩባንያ ከኢጣሊያን ውጭ ቬትናም ውስጥም የማምረቻ ኢንዱስትሪ ያለው ሲሆን፣ የስፖርት አልባሳት ለማምረት በግብአትነት በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለውን የናይሎን ወይም ሴንቴቲክ ምርት ላይ ያተኮረ ነው። ኩባንያው በአሁኑ ሰዓት ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን 23 ሄክታር መሬት ተረክቦ የሴንቴቲክ ወይም ናይሎን ፋብሪካ እየገነባ ይገኛል። የዚህ ፋብሪካ ግንባታ እስኪጨርስ ከተገነቡ የፋብሪካ ሼዶች አንዱ ላይ ምርት ለመጀመር ማሽኖችን እያስመጣ እንዲሁም ሠራተኞችን ጎን ለጎን እያሠለጠነ ይገኛል፡፡
ሌላኛው በፓርኩ ውስጥ የሚገኝ ኩባንያ ሳይ ቴክስ የተባለ ከቻይና የመጣ የአልባሳት ግብአት አምራች ኩባንያ ሲሆን፣ ማሽኖችን አስገጥሞ ሁለት መቶ የሚያህሉ ሠራተኞችን ቀጥሮ እያሠለጠነ ይገኛል። አራተኛው ኩባንያ ትራይብስ በመባል የሚታወቅ ከአሜሪካ የመጣ ሙሉ ልብስ አምራች ኩባንያ ሲሆን፣ በፓርኩ አንድ የፋብሪካ ህንፃ ተከራይቶ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነም ነው ያስረዱት።
ምክትል ኮምሽነሩ የኮምበልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርት ላይ ብቻ ያተኮረ የኢንዱስትሪ ፓርክ መሆኑን ጠቅስው፤ በተለይ በኢንዱስትሪ ፓርኩ በአገሪቱ የመጀመሪያ የሴንቴቲክ አምራች ፋብሪካዎች በመኖራቸው የቆየውን የኢንዱስትሪ ግብአት እጥረት በማቃለል ፋብሪካዎች ምርቱን ተጠቅመው እሴት የተጨመረበት ምርት እንዲያመርቱ እድል የሚፈጥር መሆኑን ያብራራሉ።
የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ ከጀመረ በኋላ የሃዋሳ ከተማ የታክስ ገቢ በአራት እጥፍ ማደጉን የጠቆሙት ዶክተር በላቸው፣ የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክም የአካባቢውን የአገልግሎት ኢንዱስትሪን በማነቃቃት ረገድ ቀጥተኛ ተፅእኖ እንደሚያሳርፍ ያመለክታሉ።
ፓርኩ በመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው እስከ 15 ሺ የሚደርስ ቀጥተኛ የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ይገልፃሉ። ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ 700 ሄክታር መሬት ስፋት የሚሸፍን ማስፋፊያ ይኖረዋል ተብሎ እንደሚታሰብ የሚጠቁሙት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ አሁን ላይ የኢጣሊያኑ ኩባንያ ፋብሪካ እየገነባበት ያለው መሬት ተጨምሮ በአጠቃላይ መቶ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ብቻ መያዙን ያስገነዝባሉ።

 

Published in ኢኮኖሚ

የግብፅ ህዝብ አምጦ የወለደው የካይሮው የጣህሪር አደባባይ ህዝባዊ አብዮት ለዓመታት በዙፋን የነበሩት የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክን ሳይወዱ በግዳቸው ወንበር በማስለቀቅ መሐመድ ሙርሲን ቢተካም፤ ሙርሲን መልሶ ለማውረድ ግን እንደ ሙባረክ ብዙ ዓመታትን አልጠበቀም፤ አልታገሰምም።
ፕሬዚዳንቱ ላይ እምነት የሌላቸው በርካታ ግብፃውያን ባስነሱት ተቃውሞ እ.ኤ.አ 2013 መንበረ ሥልጣናቸውን የተነጠቁት መሐመድ ሙርሲን ተከትሎ በዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት ወደ መሪነት ሥልጣኑ የመጡት የቀድሞው የግብፅ ወታደራዊ አዛዥ ጄኔራልና የወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ግን ለፈርኦኖቹ ሳይስማማቸው የቀሩ አይመስልም። ለዚህ ምስክር የሚሰጠው ደግሞ አልሲሲ ላለፉት አራት ዓመታት አገሪቱን በፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ ይህ ነው የተባለና ዙፋናቸውን የመነቅነቅ አቅም ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ አለመታየቱ ነው።
በአገሪቱ ታሪክ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ተከታይ እንጂ ቀዳሚ የሌላቸውና እ.ኤ.አ በ2014 ግብፃውያኑን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት 93 በመቶ የሆነ የህዝብ ድምጽ በማግኘት ኃላፊነትቱን የተረከቡት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ፤ ባለፉት አራት ዓመታት አገራቸውን ማገልገላቸውን ተከትሎ አሁን ላይ የመጀመሪያ ዙር የሥልጣን ዘመን ቆይታቸው በማብቂያው ወራት ላይ ይገኛሉ።
ግብፃውያንም ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በማካሄድ የአል ሲሲን አገልግሎት ለተጨማሪ አራት ዓመታት ለማስቀጠል አሊያም የእርሳቸውን ምትክ ወደ ሥልጣን ለማምጣት የሁለት ወራት እድሜ ብቻ ቀርቷቸዋል። በመጪው ሚያዝያ አጋማሽ የሚካሄደው ይህ አገራዊ ምርጫ ግን ገና ከወዲሁ በርካታ አወዛጋቢ ትዕይንቶችን ማሳየት ጀምሯል።
ከሁሉ በላይ አወዛጋቢና አስገራሚ የሆነው ግን በፕሬዚዳንትነት በመሰየም ወንበሩ ላይ ለመቀመጥ አል ሲሲን ለመፎካከር የደፈሩ መታጣታቸውና ደፍረው የመጡትም ቀስ በቀስና አንድ በአንድ ከውድድሩ ሜዳ ገሸሽ የማለታቸው እንዲሁም ጀርባቸው የመስጠታቸው ጉዳይ ክስተት መሆኑ ነው።
የአል ሲሲ ጠንካራና ቀንደኛ ተፎካካሪዎች እንደሚሆኑ ቢገመትም ግምቶችን ውድቅ በማድረግ ራሳቸውን ከፉክክሩ ካገለሉት መካከል የቀድሞው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አህመድ ሻፊቅ አንዱና ዋነኛው ናቸው። አህመድ ሻፊቅ ራሳቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ከምርጫው ያግልሉ እንጂ በስጋት ራሳቸውን ያገለሉም አሉ። ለዚህም እ.ኤ.አ በ1981 የተገደሉት የቀድሞ የግብፅ ፕሬዚዳንት የአንዋር ሳዳት የደም ስር የሆነው የ62 ዓመቱ ሞሃመድ አኑዋር ሳዳት ተጠቃሽ ነው። ሞሃመድ አኑዋር ግራዊ ውሳኔውን ያሳለፈው «ህይወቴ እና ደጋፊዎቼን ከአደጋ ለመጠበቅ ስል ነው›› ማለቱም ብዙዎችን አስደንግጧል፤ አስገርሟልም።
የአብዱል ፈታህ አል ሲሲ ዋነኛ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብለው ይጠበቁ የነበሩት የቀድሞ ጀኔራል ሳሚ አናንም ‹‹ያለ ፈቃድ በመወዳደር ወታደራዊ ደንብን ጥሰዋል፤ በግብፅ ህዝብና በወታደራዊ ኃይሉ መካከል ግጭት ለመፍጠር ሞክረዋል›› በሚሉና በሌሎች ተጨማሪ ክሶች የምረጡኝ ዘመቻቸው ተቋርጦ በእርሳቸውና ደጋፊዎቻቸው በግብፅ ወታደራዊ ባለሥልጣናት ወደ ወህኒ እንዲወርዱ ተደርጓል።
ግብፅ ህገ መንግሥት በጉልህ እንዳሰፈረው በአገሬው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እጩ ሆኖ ለመቅረብ ቢያንስ ከአስር ግዛቶች 25 ሺ የደጋፊዎች ፊርማና 20 የፓርላማ አባላት ይሁንታን ማቅረብ የግድ ነው። አሁን ላይ ይህን መስፈርት በማሟላት የአል ሲሲ ብቸኛ ተፎካካሪ ሆነው የቀሩት ደግሞ የ«ጋሃድ»ፓርቲው የበላይ አለቃ ሙሳ ሙስጠፋ ሙሳ ሆነዋል።
በርካታ መገናኛ ብዙኃንም፤ ምርጫው ከወዲሁ በፖለቲከኞችና በጋዜጠኞች እስር እንዲሁም የጅምላ እስራትና ታሳሪዎችን የማሰቃየት በከፋ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እየታጀበ መሆኑን አትተዋል። በተለይም መገናኛ ብዙኃን ምርጫውን በሚመለከት በሚሠሯቸው ዘገባዎች ላይ ከባድ ጫና እየደረሰባቸው መሆኑ የተገፀ ሲሆን፣ ከሁሉ በላይ የውጭ መገናኛ ብዙኃን የጫናው ሸክም አርፎባቸዋል። የአገሬው መንግሥት ‹‹የውሸት ዜና የሚያሰራጩ›› ያላቸውን መገናኛ ብዙኃንና ድረ ገፆች መዝጋቱም ታውቋል።
መሰል ክስተቶች ራስን የማግለል ውሳኔ ያስተዋሉ የፖለቲካና የመገናኛ ብዙኃንም፤ተግባሩ ከሆስኒ ሙባራክ ዘመን ጀምሮ ምርጫ ሲደርስ ብቻም ሳይሆን በሌሎችም ወቅቶች የሚከወን መሆኑን በማስታወስ፤ በአሁን ወቅት በአገሪቱ የሚስተዋለው የፖለቲካ ምህዳር ጥበትም ከዛሬ ሳይሆን ከትናንት ጀምሮ ዓመታትን ተሻግሮ የመጣ መሆኑን አስምረውበታል።
ይህ ያበሳጫቸው አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በአንፃሩ ምርጫው እንዳይካሄድ ጥሪ እስከማቅረብ ደርሰዋል። የተቃውሞው መሪ የሆኑት ሃመዲን ሳባሂም፣ ህዝቡ በመሰል ሁኔታ የታጀበውን ምርጫ በመቃወም ድምፁን ከመስጠት እንዲቆጠብና እንቢተኝነቱንም በምርጫው እለት ከቤቱ ባለመውጣት እንዲያሳይ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህን የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተግባር ግን አንዳንዶች በመልካም ጎኑ አልተመለከቱትም። በአንፃሩ «ተቃዋሚዎቹ ይህን ማድረጋቸውን ከድጋፍ ይልቅ ተቃውሞን እንደሚወልድባቸው በርካቶችም ከሰላም ይልቅ ለአመፅ ፍላጎት እንዳላቸው እንዲገነዘቧቸው ያደርጋል» ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ፕሬዚዳንት አል ሲሲ ቢሆኑም ይህ የተቃዋሚዎች ጥያቄ በእጅጉ አስቆጥቷቸዋል። ፕሬዚዳንቱ እ.ኤ.አ 2011 የተነሳውንና ለግብፃውያን አዕምሮ መጥፎም ሆነ ጥሩ ጠባሳን አትሞ የሄደውን ህዝብ አብዮት ዋቢ በማድረግ «ከሰባትና ስምንት ዓመት በፊት በዚህች ምድር የሆነውን አይነት ክስተት መቼም አይደገምም፤ ይህ እንዲሆንም አልፈቅድም» ሲሉ ተሰምተዋል።
ይህን የፕሬዚዳንቱን በብስጭት የታጀበ ንግግርና የፊታቸውን ቁጣ ያስተዋሉም አል ሲሲ በሥልጣን ዘመናቸው የተራመዷቸውን እንዲሁም የወሰናቸውን ከባድ እርምጃና እስከ ስቅላት የሚደርስ የቅጣት ውሳኔን ዋቢ በማድረግ ፕሬዚዳንቱ መሰል የህዝብ ተቃውሞ አብዮት እንዲካሄድ መቼም እድል እንደማይሰጡና በመሰል ተግባር ለመሰማራት ያሰቡ ቢኖሩም አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስዱ እርግጠኛ መሆናቸውን አትተዋል።
አሶሴትድ ፕሬስ፣ አገሬው ምርጫ በቀደመ አካሄድ ጉዞው ላይ መሆኑንና የአንድ ግለሰብ ብቻ መሆኑን በመግለፅ አል ሲሲ በምርጫው ማሸነፋቸው እርግጥና ሃቅ ነው ብሎ ሲዘግብ፣ የአልጀዚራ ጂሊያን ካስተለር ሀታተም፤ የአገሬው የፖለቲካ ምህዳር ጠባብ መሆኑንና ፓርቲዎችም ሰውዬውን መፈተንና መፎካከራቸው የማይታሰብ መሆኑን በማስታወስ፤ አል ሲሲ ዳግም አገሪቱን መምራታቸው እርግጥ መሆኑን አስነብቧል።
የአብዱል ፈታህ አል ሲሲ ብቸኛ ተፎካካሪ ሙሳ ሙስጠፋ ሙሳ ግን ግልፅ፣ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ የሚካሂድ ከሆነ ለአሸናፊነት እንደሚተጉ በመወትወት ከሁሉ በላይ የምርጫው ፍትሃዊነት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል። የአገሬው ምርጫ ቦርድም ይህን የሙሳ ሙስጠፋ ሙሳ ፍላጎት ከሁሉ በላይ ለአገሬው ህዝብና ዴሞክራሲ ክብር፣ ምርጫው ግልፅ፤ ነፃና ፍትሃዊ እንደሚሆን ቃሉን ሰጥቷል። አል ሲሲም ቢሆኑ ግብፃውያኑ በምርጫው የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉና መሳታፍ ብቻም ሳይሆን ‹‹ይሆነኛል፤ ይበጀኛል›› የሚሉትን ያለ ተፅእኖ በፍላጎታቸው እንዲመርጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ፐብሊክ ሬዲዮ ኢንተርናሽናል ፀሐፊ ሰልማን ኢስላም ግን አብዱልፈታህ አልሲሲ በፕሬዚዳንትነት ውድድሩን ብቻቸውን ተወዳድረው የራሳቸው ተፎካካሪ ከመሆን ያዳኗቸው ሙሳ፤ በሚያስቅ መልኩ የአል ሲሲ ተቃዋሚ ከመሆን ይልቅ ደጋፊያቸው ናቸው። ለዚህም የኋላ ታሪካቸውን መለስ ብሎ መቃኘት በቂ መልስ ይሰጣል የሚል ሐተታን አስፍሯል።
ይህ ምን ያህል ተዓማኒ ነው የሚለውን ለማረጋገጥ የቀረቡ መረጃዎች ግን ብዙ ሚዛን የሚደፉ አልሆኑም። ሙሳም ቢሆኑ ‹‹ተቃዋሚ ሳይሆኑ ደጋፊ ናቸው›› ሲባል የቀረበባቸውን ትችት በሚመለከት አል ዮሁም አል ሳባ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ ‹‹እኛ ወደ ምርጫው የገባነው እንደ አሻንጉሊት አይደለም» በማለት መልሰዋል።
ይህ በብዙ አስገራሚና አወዛጋቢ ሁነቶች የታጀበ ምርጫ የክንውን ቀነ ቀጠሮን በመጪው ሚያዝያ ያደርጋል። ከወራት በኋላም፤ ግብፃውያኑ በድምፃቸው ድምር ውጤት የአል ሲሲን አገልግሎት ለተጨማሪ አራት ዓመታት ያስቀጥላሉ። አሊያም ምትካቸውን ወደ ሥልጣን ማምጣታቸው በይፋ ይታወቃል።

 

Published in ዓለም አቀፍ

የፅሑፌ መነሻ አጩሌ (የአሜሪካው ግቢ ከኢህአዴግ ሜዳ) በኢህአዴግ ሜዳ አውራጅና ጫኝ ለምን በዛ? በሚል ርዕስ ያቀረበው ፅሑፍ ነው። ፀሐፊው የእነሱ ባልሆነው የኢህአዴግ ሜዳ ላይ እንዳሻቸው ሲፈልጡና ሲቆርጡ የሚውሉ የህልም ፈላስፎችን በኢህአዴግ ውስጥ ከተፈጠረው ችግር ጋር አያይዞ አሳይቶናል። ፅሑፉ በውስጥም በውጭም ያለውን ለመዳሰስ የሞከረና የወቅቱን ነባራዊ ሁኔታ በትክክለኛ ትዝብት በግላጭ ያሳየ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የኢህአዴግ ውስጥስ ምን ይመስል ይሆን በሚለው ላይ አትኩሬ እና በፀሐፊው እይታ ላይ ተመስርቼ ለማየት እሞክራለሁ።
ህዝብን አለማክበር፣
የእኛ የፓርላማ አባላት፣ እንደ ሌሊት ወፍ ቀን ቀን አይጥ፣ ሌሊት ሌሊት ወፍ አንሆንም ብለው ለቆሙለት ፕሮግራምና ፕሮግራሙን አምኖ ለመረጣቸው ህዝብ በፅናት በመቆማቸው፣ ነፍሳቸውን ይማረውና የሙታኖቹ ፅንፈኞች መዘባበቻ ሆነዋል። ይሄ የህዝብ ወኪሎቻችን የሆኑት የምክር ቤት አባላት የመጀመሪያ ድል ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ የዴሞክራሲ ማስፋትና ለዴሞክራሲ መስፋት አዕማድ ለሆኑ መሰረቶች እጅግ በብዙ ለመሥራት እልህ ሊገቡና መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ እንዲሆኑ የሚያነሳሳቸው ነው። በታሪክ አጋጣሚ የፅንፈኞች የውስልትና ጫናና ማባበያ ለፓርላማችን የመጀመሪያው ነው።
ፓርላማችን የህዝቡ ጥያቄ አገሪቱ ውስጥ እየታየ ካለው እድገት በላቀ ሁኔታና ደረጃ በደረጃ እያደገና እየሰፋ መምጣቱን ተገንዝቦ በተለይ በመልካም አስተዳደር፣ አገልግሎት አሰጣጥና ታላላቅ የመሰረተ ልማት ግንባታ ጉዳዮች አስፈፃሚውን በገለልተኝነት ዕለት ተዕለት መከታተሉን ባጠናከረበት በዚህ ሰዓት ምክር ቤቱን ለማሳነስ የወሰኑ ፅንፈኞች ሞራል ከሚነካ ትንኮሳቸው ባለፈ ለማስፈራራት ያደረጉት ሙከራ አዋራጅ ነው። የፅንፈኞቹን ስለ ምክር ቤቱ የአሰራር ሂደት ያላቸውን እውቀት አልባነትም ያጋለጠ ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ የደጋፊ፣ የተቃዋሚ ሳይባል የሁሉንም ህዝቦች ጥቅም ለማስጠበቅ የሚሰሩትን የህዝብ ተወካዮች በዚህ ደረጃ መፈረጅ መላውንም ህዝብ በግላጭ የናቀ በመሆኑ በህግ ተጠያቂ መደረግ ያለበት አካል እንዳለም የሚያሳይ ነው።
የመስመር ተቃርኖ፣
በአገሪቱ ሰፋ ባሉ አካባቢዎች ለረጅም ጊዜያት ተከስቶ የቆየው የሰላም እጦት በዋናነት በሰላም ወዳዱ ህዝብ፣ በአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች ተሳትፎ እየከሰመና እየበረደ በመጣበት ሰዓት፣ ፅንፈኞቹ አደራጅተው በቀጥታ የሚያሰማሯቸው ኃይሎች በየአካባቢው ህዝብ ላይ የሚያሳድሩትን ጫና ተከታትሎ ለማስቆም መንግሥት እንቅስቃሴ ማድረጉ ያሰጋቸው የህዝብ ጠላቶች የፀጥታ መሰናክል ለመሆን ሁሉንም አይነት የጥፋት አማራጭ ለመጠቀም ርብርባቸውን አጠናክረዋል።
ከእነዚህ ውስጥ የኢህአዴግ አካላትን ከቆሙለት ዓላማ ነጥለው የጥፋታቸው አጃቢ እንዲሆኑ የማድረግ እንዲሁም የአባላትን ሚናና ወሳኝነት በማሳነስ የጥፋታቸው የዳር ተመልካች እንዲሆኑ ማድረግ ይጠቀሳል። ከአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች በህዝብ ምርጫ ፓርላማ የገባውንና 547 አባላት ያሉትን የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህዝብ ሳይመርጠውና የህዝብ ወኪል ሳይሆን ኮሮጆ ሰርቆ የገባ ነው በሚል ያፈጠጠ ውሸት የህዝብንና አገርን ክብር የሚነካ አዋራጅ ተግባር ሲፈፅሙም ታይተዋል።
በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል የሚካሄደውን የሊቀመንበርነት ምርጫ ለተሻለ ተልዕኮ መፈፀምና ቀድሞ ለመሰዋት ከሚደረግ ግንባር ቀደምነት ይልቅ፣ በተንሸዋረረ የዘረኝነት ምልከታና ስዕል አባል ድርጅቶቹ እርስ በእርስ እንዲጠራጠሩና ለብተና እንዲጋበዙ በማድረግ በአገሪቱ መቆሚያ የሌለው አለመረጋጋት እንዲከሰት በከፍተኛ ደረጃ እየተረባረቡ መሆኑ እየታየ ነው።
ይህንኑ የተወላገደና የተንሸዋረረ አስተሳሰብ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፣ አልፎ አልፎም የድርጅትን መርህ ፊት ለፊት በመፃረርና በመጣስ በተለያየ መልኩ የሚያራምዱ አንዳንድ አመራሮችን እያየን ነው። ጎራ መቀላቀሉ እንዲህ ሰፊ በሆነበትና መስመር ለይቶ በቆመለት ማህበራዊ መሰረትና በራስ የድርጅት አጥር የማይንቀሳቀስ አመራርና አባል እየሰፋ በመጣበት ሁኔታ ችግሮቹ መታየታቸው አስገራሚ ባይሆንም፣ ለኢህአዴግ እና የኢህአዴግ አባል ለሆነ አመራር የማይመጥን ተርታ ህዝበኝነትና የመስመር ጥሰት አለመቆሙ ግን አደገኛ ሁኔታ ላይ እንዳለን ያረጋግጣል።
ህዝባዊነት ድንበር የለውም ብሎ በሚያምነው ኢህአዴግ ውስጥ ተሰልፎ የመንግሥት ሥልጣንን የብሔሩ ህዝብ ሳይሆን በብሔሩ ስም ለመነገድ የሚሞክር የኢህአዴግ ሰው በድርጅቱ ታሪክ ታይቶ አያውቅም። የኢህአዴግ መስመር ከሌሎች ተፎካካሪ ወይም ተቃዋሚ ፓርቲዎች መስመር እንደሚለይ የማያውቅ የኢህአዴግ አመራር በድርጅቱ ታሪክ ተሰምቶና ታይቶ አያውቅም።
ቀድሞውኑ ተቃዋሚ ወይም ከኢህአዴግ ጋር ተፎካካሪ የሆነው ፓርቲ የመስመር ልዩነቱን ይዞ፣ የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥትን አተያይ ተቃርኖና ይህን ተቃርኖውንም በምርጫ ጭምር ሞክሮ በመሸነፉ ተነጥሎ ሳለ እኛና እነሱ ልዩነት የለንም የሚል አስተሳሰብ በእርግጥ የኢህአዴግ ነው ወይ የሚል ጥያቄም ያስነሳል። በእርግጥም ህዝበኝነቱና ጎራ መቀላቀሉ አይሎ እዚህ ደረጃ ከደረሰ ድርጅቱ ራሱን አሁን እያየ ካለውም በላይ በጥልቅ መፈተሽ እንዳለበት ያመላክታል።
ከየት ወዴት?
የኢትዮጵያ ህዝብ በትግሉ ያመጣውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከመመስረቱ በፊት በብሔሩ ተጨቁኗል። በብሔሩ ተሰዷል። በማንነቱ ተዋርዷል። በዘሩና በአመጣጡ ተሸማቋል። እኩል ሆኖ ለመኖር ስሙን ጭምር ቀይሯል። በቋንቋው ተገፍቷል። በኢኮኖሚ አቅሙ ከተርታም ተርታ ሆኖ ለከፋ ረሃብና ጉስቁልና ተዳርጓል። የኢኮኖሚ መድልኦና መገለልም አሳልፏል። የኢትዮጵያና ኢትዮጵያን የሰሯት ብሔሮች ብሔረሰቦች የረጅም ዘመናት ታሪክ ይህም ጭምር ነው።
የኢትዮጵያ ህዝቦች የመሰረቱት ህገ መንግሥታዊ ሥርዓት በቅድሚያ እነዚህን የጭቆና ገመዶች የበጣጠሰ፣ የራስን በራስ የማስተዳደር ሥርዓት ያወጀ፣ ማንም ተጨቁኖ ሊኖር እንደማይችል ዋስትና የሰጠ፣ ለጋራ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ልዩ ትኩረት የሰጠ፣ ለህዝቦች ብልፅግና፤ ፍትሃዊና እኩል ተጠቃሚነት የቆመ ምርጥ ህገመንግሥታዊ ሥርዓት ነው።
የኢትዮጵያ ህዝቦች የመሰረቱት ሥርዓት ብዙኃን የበላይ፣ ውህዳን የበታች የማይሆኑበት ልዩ የእኩልነት ሥርዓትም ነው። ሥርዓቱ ብዝሃነትን በቁጥር አይቶ የበላይ እንደማይለው ሁሉ፣ ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች አገር በመሆኗ በብሔር ብዛት አይቶም አንዱን የበላይ ሌላውን የበታች የማያደርግም ነው፤ ከብሔር አንፃር ትልቁ ኢትዮጵያ 56 ብሔሮች ያሉት ደቡብ ክልል ነውና። ሥርዓቱ የቆዳ ስፋትንም አይቶ ትልቁ ክልል ብዙ ጥቅም ማግኘት አለበት አይልም። እንዲያ ቢሆን ኖሮ ትልቁ ክልል የኢትዮጵያ ሶማሌ ነበርና። የሥርዓቱ ልዩ ባህሪ እኩልነትን የሚያስተናግድበት ልዩ ሁኔታም ጭምር ነው። ማንም የበላይ፣ ማንም የበታች እንዳይሆን ያደረገ ነው የሚባለውም ለዚህ ነው።
በአንድ በኩል እኩልነቱ ህመም የሆነባቸው በህዝብ ስም ሲነግዱ የኖሩ ገዥዎች፣ በሌላ በኩል የጭቆና ሥርዓቱን ንዶ እኩልነቱን ያረጋገጠው መላው ህዝብ መሆኑን ያልተቀበሉ ጠባቦች የኋላ ታሪክ መዝዘው እንደ ጅብና አህያ ሲበላሉ እንዳልከረሙ ሁሉ ሥርዓቱን ሚዛናዊነት አሳጥተው ለማፍረስና ህዝቡን ለብተና ለመዳረግ የእውር ድንብራቸውን ሲንፈራገጡ ይታያሉ።
በግል የወንበርና የሥልጣን አተያይ ላይ በነበራቸው ጥልቅ የግል ጥቅም መሻት ቁጭት ላይ ሆነው የእነሱ ከፍታ የህዝቡ ከፍታ እንደሆነ አድርገው በመሳል በብሄርና በማንነት ስም ሲነግዱ ይታያሉ። ታሪክ ራሱን ይደግማል እንዲሉ በጭቁኑ የአማራ ህዝብ ስም ለዘመናት ሲነግድ የኖረው ስዩማዊና መሥፍናዊ ሥርዓት፣ ይልሰው ይቀምሰው ያልነበረው ጭቁን የአማራ ህዝብ በሌሎች ህዝቦች ዘንድ የሥልጣን ባለቤትና ገዥ እንደሆነ አድርጎ ሲያቀርበው ቆይቷል።
በዚህም ምክንያት አማራው እንደ ገዥ መደብ ተቆጥሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በተበተነበት አካባቢ ፍዳውን ሲያይ ቆይቷል። አማራው እንደ ሌላው ህዝብ ሁሉ ሲጨቆንና ሲረገጥ እንደቆየ ለማስረዳት የህዝብ ለህዝብ ትውውቁን ማስፋት ባይቻል ኖሮ ቁርሾው በቀላሉ የማይሽር ይሆን እንደነበር የማይካድ ነው።
የህዝበኝነት በሽታ፣
አሁንም በኢህአዴግ አባል ድርጅት ውስጥ ጭምር ሆነው በህዝብ ስም ሥልጣንን የመፈለግ ኢህአዴጋዊ ያልሆነ አባዜ ህዝባዊ ያለመሆኑን ፊት ለፊት መነጋገርና መተማመን ያለባቸው እራሳቸው ኢህአዴጎች ናቸው። ህዝበኝነት የህዝብ ጠላትነት መሆኑን በግልፅ በመተማመን በህዝባዊ አተያይ አብሮ ለመጓዝ በግላጭ መነጋገር ያለባቸው እራሳቸው ኢህአዴጎች ናቸው።
ኢህአዴግ የሚመራው መንግሥት በህዝባዊ አተያዩ ድንበር የለሽ መሆኑን ለደቡብ ሱዳን ሰላም መረጋገጥ እዚያው ድረስ ሄዶ ዋጋ እየከፈለና እየሰራ፣ የሶማሊያን ሰላም ለማረጋገጥ በቦታው ተገኝቶ ዋጋ እየከፈለ፣ የጎረቤት አገር ስደተኞችን ከጦርነትና ትርምስ ጠብቆ በአገሩ እየተቀበለና ይህንኑ በተግባር እያረጋገጠ ባለበት በዚህ ወቅት የኢትዮጵያዊነታችን አዕማዶችና ሙላቶች የሆኑት ሁሉም ብሔረሰቦች ያለ አንዳች ስጋት በአገራቸው ሁሉም ቦታዎች መኖርና መሥራት ያለመቻላቸው የህዝበኝነቱ መሸርሸር ብቻ ሳይሆን የህዝበኝነቱ በሽታ ያመጣው ነው።
በኢህአዴግ መስመር ላይ መሆኑን የዘነጋ የኢህአዴግ አመራርና አባል አብዮታዊነት ወዴት እያመራ እንደሆነም ማሳያ ነው። ለዚህም ነው በእኛና በተቃዋሚዎቹ መሃል የመስመር ልዩነት የለም የሚል የኢህአዴግ አባል ተፈጥሮ እያየን ያለነው። በሽታው በመቻቻልና በመከባበር ሳይሆን በመማማርና በመቆራረጥ ሊድን እንደሚገባ በጥልቅ መመካከርም የሚያስፈልገው።
የህዝበኝነቱ በሽታ በቶሎ መዳን ካልቻለና ህመሙ የሚቀጥል ከሆነ በቅድሚያ የሚበላው በሽታው ያለበትንና የሚያስታምመውን አካል መሆኑን መረዳትም እጅግ ወቅታዊ ሆኖ ይታያል። የጅብ ተረት አላብዛና ጅብ የራሱ ቁስል የሌላ እየመሰለው በልቶት ይሞታል እንዲሉ፣ የቆሙበትን ማህበራዊ መሰረት ዘንግቶ፣ ራስን ከማየት ይልቅ በሩቅ ያለን እያሳዩና ችግርን ወደ ውጭ እያደረጉ በሥልጣንና መሰል ጥቅሞች ታጥሮ ከዋናው ችግር ጋር የመኖሩ ሂደት ብዙም በህዝብ ውስጥ አያቆይም።
ይልቁንም ይህን እድል በአግባቡ በመጠቀም፣ በህዝባዊ አተያይ መርህ ላይ በመቆም ድህነትን ለማሸነፍ በቀን ከለሊት እሩጫ ለራሱ፣ ለህዝቡ፣ ለአገሩ እድገትና ብልፅግና እየሠራ ያለውን፣ የብልፅግና ተስፋ ያሳየነውን ሁሉንም ህዝብ የሁላችንም አለቃ መሆኑን በተግባር መሪው ሳይሆን ተመሪው ሆነን ብናረጋግጥ መልካም ነው።

ናፍቆት አሰፋ

Published in አጀንዳ

ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በአገራችን ጥቂት በማይባሉ አካባቢዎች የህግ መጣስና የሰላም መናጋት ስር እየሰደደ መምጣቱ ከአብዛኛዎቻችን የተሰወረ አይደለም፡፡ እየተፈጠረ ያለው ሁከትና ብጥብጥም ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዳይገቡ እያደረጋቸው በመሆኑ የስጋት ህይወት እንዲገፉ ጫና ሲያሳድርባቸው ቆይቷል፡፡ ችግሩ ከሰላም መደፍረስ ባለፈ የበርካታ ዜጎችን ህይወት ቀጥፏል፡፡ በስንት ጥረት ያፈራናቸውን የአገሪቱ ሀብትም አውድሟል፡፡ የብዙ ዜጎችን ሀብትና ንብረታቸውን አሳጥቷል፤ ተወልደው ያደጉበትንም ቀዬ ለቀው እንዲወጡ አስገድዷል፡፡
ከምንም በላይ ደግሞ የአገሪቱ ዜጎች ሁሉ እኩል መብት እንዲኖራቸውና መብታቸውንም ሆነ ግዴታቸውን በነጻነት እንዲተገብሩ ያስቻላቸውና የሚያስችላቸው የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ህገ መንግሥትና ህገ መንግሥታዊው ሥርዓት ለአደጋ ተጋልጦ ከርሟል፡፡ ይህም እየሆነ ያለው የተፈጠረው የሰላም መደፍረስና የማን አለብኝነት እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ በመምጣቱ ሲሆን፣ ጉዳዩንም በመደበኛው የህግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠርና ሀይ ለማለት ከአቅም በላይ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ይህን ተከትሎ የኢፌዴሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ህገ መንግሥቱንና ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከአደጋ ለመከላከልና ዜጎች ያለምንም ስጋት ህይወታቸውን እንዲመሩ ሲል የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉ ይታወሳል፡፡ ይህንኑ አዋጅ፣ በእረፍት ላይ የነበረው የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰሞኑን በአስቸኳይ ተጠርቶ ባካሄደው ስብሰባው በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በመወያየት መርምሮ ማጽደቁም ይታወቃል፡፡ ይህ አዋጅም ለስድስት ወራት የሚቆይ ሲሆን፣ ከመጠናቀቁ በፊትም የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስቱ የአዋጁ ተፈጻሚነት ቀሪ የሚሆንበትን ጊዜ ሊወስን እንደሚችልም በአዋጁ ተጠቅሷል፡፡
የአዋጁ መውጣት ያሰፈለገበት ዋና ዓላማ የህዝቦችና የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች እየተጣሱ በመሆኑና መንግሥትም ይህንን ለማስከበር እንደተለመደው በመደበኛው የህግ ማስከበር ሥርዓት ማከናወን ባለመቻሉ ነው፡፡ ጉዳዩን በዝምታ ማለፍ ያለመቻሉ ሌላው ምክንያት ደግሞ በፀረ ሰላም ኃይሎች ጥቂት የማይባሉ መንግሥታዊና ህዝባዊ አገልግሎቶች እንዲቋረጡ በመደረጋቸው፣ የትራንስፖርት አገልግሎቶችም በኃይል እንዲቋረጡ በመደረጋቸውና ተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት በመድረሱም ጭምር ነው፡፡ በብዙዎቹ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ ቀላል የማይባል ውድመት ከመድረሱም በላይ ዜጎች በብሔራቸው የተነሳ ለከፍተኛ ጉዳት እየተዳረጉና የአገራችንም ኢኮኖሚ አደጋ ላይ የመውደቁ አዝማሚያ በመታየቱ ነው፡፡
በእርግጥ አዋጁ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውይይት ቀርቦ በነበረበት ወቅት ከፍተኛ የሐሳብ ፍጭት ተደርጎበት እንደነበር ይታወቃል፡፡ ጥቂት የማይባሉም የምክር ቤቱ አባላት ሰላም ባለበት ቀጣና፣ የአዋጁ መውጣት አላስፈላጊ ነው ወይ? ብለው ሐሳብና ጥያቄ ቢሰነዝሩም፤ በየጊዜው በአንዳንድ አካባቢዎች የሰው ህይወት እየጠፋና ንብረት እየወደመ ስለመሆኑ ግን ከማንም የተሰወረ አልነበረም፡፡ በሌላ በኩል ግን በሐሳብ ፍጭቱ ወቅት የተነሱ ገንቢና አስፈላጊ አስተያየቶችም በመኖራቸው በአዋጁ የሚካተቱ ሆነው በመገኘታቸው እንደተወሰዱም ተጠቅሷል፡፡
እንዲያም ሆኖ ግን በምክር ቤቱ የተንጸባረቁ አስተያየቶችና የተለያዩ ሐሳቦች የፓርላማውን ዴሞክራሲያዊ አካሄድ የሚያሳይ በጎ ጅምር መሆኑን ያመላከቱ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ በመቃወምም ሆነ ድምጻቸውን በመንፈግ ስጋታቸውን የገለጹ የምክር ቤቱ አባላት፣ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም ሐሳባቸውን በነጻነት መግለጽ የመቻላቸውም ነጸብራቅ ነው፡፡ ይሁንና ህግ ጉልበተኛውንም ሆነ ጨዋውን በእኩል የሚዳኝ የፍትህ ሥርዓት እንደመሆኑ ከስጋት በመውጣት ለህግ የበላይነት ዘብ ሊቆሙ ይገባል እንላለን፡፡
መንግሥት የአንድ አካባቢ ጠባቂ ብቻ ሳይሆን የሁሉም እንደሆነ መዘንጋት የለብንም፡፡ ህግ ባለበት አገር ዜጎች ሊሸማቀቁና መውጪያ መግቢያው የገደል ያህል ሊያስፈራቸውም አይገባም፡፡ ጥያቄን ህግ ሳይጥሱ ማቅረቡ እንደተጠበቀ ሆኖ ነገር ግን ሥርዓት አልበኞች የህግን የበላይነት እንዲሸረሽሩ ሊፈቀድላቸው አይገባም፡፡ ሥርዓት አልበኝነትን መንግሥት ሀይ ማለት የማይችልበት ደረጃ ላይ ከደረሰ ግን ለዓመታት የተገነቡ መሰረተ ልማቶችና የልማት አውታሮች በአንዳፍታ ከመጥፋታቸውም በላይ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ህይወት እንደዋዛ መርገፉ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህም መንግሥት ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› የሚለውን ብሂል በመተግበር ህዝቡንና ዜጋውን መታደግ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ጉዳይ እንዳልሆነ ሊረዳ ይገባል፡፡
አገር እንደ አገር መቀጠልም መልማትም የምትችለው ሰላሟ ሲጠበቅ ነው፡፡ ለሰላሟ መጠበቅ ደግሞ ዋናውን ሚና የሚጫወተው ጋራ ሸንተረሩ አሊያም እንስሳቱና አዕዋፋቱ ሳይሆኑ ክቡሩ የሰው ልጅ ስለመሆኑ ለአፍታም ቢሆን ሊዘነጋ አይገባም፡፡ በእርግጥም ይህን ለማድረግ በመጀመሪያ የመከባበር፣ የመተሳሰብ፣ የመተዛዘንና የመደማመጥን ቁርጠኝነትን ይጠይቃል፡፡ የአንድ አገር ህዝቦች እንደመሆናችንም የእርስ በርስ ሽኩቻን በማጥፋት የአብሮነት እሴቶቻችንን በቀናነት ልናጎለብት ይገባናል፡፡
አዋጁም ቢሆን ከሚከለክላቸው ነገሮች አንዱን መጥቀስ ካስፈለገ ማንኛውም ሁከት፣ ብጥብጥና በህዝቦች መካከል መጠራጠርና መቃቃር የሚፈጥር ይፋዊም ሆነ የድብቅ ቅስቀሳ ማድረግን ነው፡፡ ሌሎችም በአዋጁ ውስጥ የተካተቱ ጉዳዮች ዋነኛ ዓላማቸው የህዝብንና የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ፣ ኢንቨስትመንትና መሰረተ ልማቶችን ከጥቃት ለመጠበቅና አስተማማኝ ሰላምን በመላ ሀገሪቱ ማስፈን መሆኑ በቀናነት ሊታሰብ የሚገባው ነገር ነው፡፡ አዋጁም የህጎች ሁሉ የበላይ ከሆነው ከኢፌዴሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 93 ንዑስ አንቀጽ 1 ‹‹ሀ›› ላይ ባለው መሰረት የወጣ በመሆኑ ህጋዊ መሰረት እንዳለውም ልብ ሊባል ይገባል፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ወቅት በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 ንዑስ አንቀጽ 5 መሰረትም ሰባት አባላት ያሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአባላቱና ከህግ ባለሙያዎች መርጦ የሚሰይም እንደመሆኑ ይህንኑ ተግብሯል፡፡ ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ፣ ሥራውን ማስተዋል በተሞላበት መንገድ ማከናወንና ቅሬታ ሊፈጥሩ የሚችሉ ድርጊቶችን በቀናነትና በጥንቃቄ ማየት የግድ ይለዋል፡፡ በየደረጃው ያለው አዋጁን አስፈጻሚም ሆነ ፈጻሚው አካል ህጉ በአግባቡ ስለመተግበሩ መከታተልና መቆጣጠር እንዲሁም አዋጁን በመተግበርና በማስተግበርም የበኩላቸውን አገራዊ ሚና ሊወጡ ይገባል፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

አዲስ አበባ፡- ፖርቹጋል ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት ለማጠናከር እንደምትፈልግ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናገሩ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ ትናንት የአውሮፓ ህብረት የውጭ ግንኙነት ክፍል ምክትል ኃላፊንና የፖርቹጋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ፖርቹጋል ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት ለማጠናከር እንደምትፈልግ የፖርቹጋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሪቤርዮ ከሚኒስትር ዴኤታዋ ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ለረጅም ዘመናት የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውንም አመልክተዋል። በግብርና፣ ባህልና ቱሪዝም መስኮች ላይም ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ትብብር ማጠናከር እንደሚፈልጉም ገልጸዋል።
በተያያዘ ዜና የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ግንኙነት ክፍል ምክትል ኃላፊ ክርስቲያን ሌፍለርና የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታዋ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች፣በአካባቢያዊ ሁኔታዎችና ኢትዮጵያ በምትቀበላቸው ስደተኞች ላይ የሚደረገውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት መንገድ ላይ መነጋገራቸውን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአውሮፓ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ አስታውቀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም፣ ሚኒስቴር ዴኤታዋ ከሁለቱም አካላት ጋር ያደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ ከፖርቹጋልና ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከር በምትችልበት ጉዳይ ላይ መምከራቸውን አመልክተዋል። በሁለትዮሽና በአፍሪካ ቀንድ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
በውይይቱም ኢትዮጵያና ፖርቹጋል ያላቸውን ጥንታዊ ግንኙነት መሠረት አድርገው ይበልጥ መተባበር አለባቸው የሚል መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል። ‹‹ፖርቹጋል በግብርና መስክ የአገር ውስጥ የሰው ኃይልን በሰፊው የሚያሳትፍ የረጅም ጊዜ ልምድ አላት›› ያሉት ቃል አቀባዩ፣በመስኩ ይበልጥ ለመተባበርና ፖርቹጋል ብቁ የቱሪዝም የሰው ኃይል በመፍጠር ረገድ ያላትን ተጠቃሽ ልምድ ለመቅሰም መግባባታቸውን አስታውቀዋል፡፡

በሪሁ ብርሃነ

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።