Items filtered by date: Wednesday, 07 March 2018

ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ የመጣው የጀግንንት ስሜት በየዘመናቱ ለትውልድ እየተላለፈ ቆይቷል። ይህ ዕውነትም በተለያዩ ጊዜያት አገራችንን ለመውረር በመጡ ጠላቶቻቸን ላይ ሲንጸባረቅ መኖሩ ዕውነት ነው። አሁን በምንገኝበት ዘመንም ህፃናት የመላው አፍሪካ ድል መታሰቢያ በሆነው ዕለተ ዓድዋ ጥንታዊውን የጀግኖች አርበኞች አለባበስን በማስታወስ እንዲህ ቀኑን ዘክረውት አልፈዋል። «ክብር ለጀግኖች አርበኞቻችን»
(የሳምንቱ ፎቶ)

Published in መዝናኛ
Wednesday, 07 March 2018 17:05

ደፋርና ጭስ...

መቼም ወዳጆቼ! የሀገራችን ተረትና ምሣሌዎች እንዲህ እንደዋዛ ያለምክንያት የሚነገሩ አይምሰሏችሁ። የቀደሙት  ሰዎች እኮ ከደረሰባቸው ደግና ክፉ አጋጣሚ ተነስተው ነው አባባሎቹን ሲጠቀሙባቸው የኖሩት። ምን እነሱ ብቻ ይህ  እውነት ለዘመናችንም  ተርፎ ዛሬ ላይ እኛም በየአጋጣሚዎቹ እንተርታለን።
ለምሳሌ «ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም» የሚለውን አባባል ብንወስድ ነጥብ ታህል ቀደዳ የሌለው በሚመስል ግርግዳ መሀል ድንገት መንገድ ጥሶ የሚወጣን ጭስ ከአንድ ብርቱና ደፋር ሰው ጋር ልንመስለው እንችላለን። አንዳንዴ ግን ይህ አይነቱ  አባባል እንደ ግብሩ  ሳይሆን ቀርቶ በተቃራኒው የሚገኝበት ሁኔታም ይኖራል። እንዴት? ካላችሁኝ ደግሞ ሰሞኑን በእኔ ላይ የደረሰውን የደፋሩንና የጭሱን አጋጣሚ እነሆ።
ከቀናት በፊት የአጋጣሚ ጉዳይ እግሬ መሀል ሜክሲኮ አደባባይ አደረሰኝ። ሰዓቱ ገፍቷል፤ ምሽቱ ድንገት መጣል ከጀመረው ዝናብ ጋር ተዳምሮም ፍርሀት የሚመስል ስሜት  ውስጥን ይፈትናል። ወይጉድ! አሁንም  ስለድፍረት እየተወራ ስለፍርሀት መወሳቱ ለምን? ትሉኝ ይሆናል። እኔም እኮ እሱን ልነግራችሁ ነው። ጥቂት ብቻ ታገሱኝ።
በዚህ ሰዓት ሊያጋጥም የሚችልን የትራንስፖርት ችግር እያሰብኩ ነው። ዝናቡንና የሰሞኑን ኃይለኛ ዝናብ ምክንያት አድርጎ መብራት ከጠፋ ደግሞ ስጋቴ ይበልጥ ይጨምራል። እኔ ደግሞ ጥሎብኝ መብራት ሲጠፋና ጨለማ ሲበረታ አልወድም። ይህንኑ እያሰላሰልኩ በርከት ያሉ ሰዎች ወዳሉበት አንዱ ጥግ አመራሁ። ጥቂት እንደቆየሁም   አካባቢው በሚገርም ፍጥነት በርከት ባሉ አውቶቡሶች ተጥለቀለቀ።
ከታክሲዎቹ ይልቅ የአውቶቡሶቹ ፈጥኖ መድረስ እጅግ አስገርሞኛል። በዕለቱ ምርጫና ፍላጎት ከተገጣጠመ ባሻው ተሳፍሮ መሄድ የሚገድ አይሆንም። እኔም ዓይን አዋጅ ከሆኑብኝ አውቶቡሶች መሀል የትኛውን ከየትኛው እንደምመርጥ እያሰብኩ  ቆየሁ። ከነዚህ  ሽንጠ ረጃጅም ተሽከርካሪዎች በተለየ ትኩረቴን የሳበው አንዱ ሆነና ትኬት ቆርጬ ለመጓዝ ጠጋ አልኩ።
በቅርቡ በአንድ ደረጃ ከፍ ብለው ከመጡት የከተማችን አውቶቡሶች አንዱ ነው። ዕድሜ ለጊዜ ይሁንና ባደጉት አገራት ስናያቸው የነበሩትን የከተማ ባቡሮችና እነዚህን መሰል አውቶቡሶች  እኛም መጠቀም መቻላችን ያስደስታል። በተለይ ደግሞ ይህ አውቶቡስ ግርማ ሞገሱ ያምራል። ግዙፍ መሆኑና ብዙዎችን በአንድ አቅፎ መያዙም  ተመራጭነቱን ያጎላዋል። ያልተለመደና አዲስ መሆኑም ከነባሮቹ  በተለየ ዓይን ውስጥ እንዲገባ  አስችሎታል።
  እኔም በእነዚህና በሌሎች መሰፈርቶቹ ሳልማረክ አልቀረሁም። በተለይም ከውጭ ብቻ ሳየው የቆየሁትን ወደ ውስጥ ዘልቄ ብጎበኘውና አረፍ ብዬ ብጓዝበት አልጠላም። ወደበሩ ጠጋ ብዬ ትኬት እንደቆረጥኩ  እምብዛም ሰው ያለመኖሩን  ተረዳሁ። ይሄኔ  ምርጫዬን ከታችኛው ይልቅ ወደ ላይኛው ቀይሬ  በደረጃው ሽቅብ ተጓዝኩ።
አውቶቡሱን የሚጠቀም ማንኛውም መንገደኛ እላይ ደርሶ ወንበር መያዝ ግዴታው ነው። በዚህ ስፍራ መቆምም ሆነ በደረጃው ላይ መቀመጥ  ፈጽሞ የተከለከለ ነው። ይህ  ግዴታ ስለመሆኑም ከአውቶቡሱ አሽከርካሪ (ካፒቴን) ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ስለሚደርስ ማንም ህጉን ሲተላለፍ አላስተዋልኩም። በጠባቧ ደረጃ ወደ ላይ አልፌ ጥግ ላይ እንደተቀመጥኩ ቦታው በአንዴ በተጓዞች ተሞላ። ጥቂት ቆይቶም አውቶቡሱ ተንቀሳቀሰና መንገዱ ተጀመረ። ጉዞ  ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ።
ወዳጆቼ! አሁን ከላይ ሆኜ በግርምታ አንጋጠው የሚያዩኝን ሁሉ ቁልቁል መቃኘት ጀምሬአለሁ። ይህን የማደርገው ደግሞ እኔ ብቻ አልምሰላችሁ። አብዛኛው በተመሳሳይ ስሜት ሆኖ ተሽከርካሪዎችና እግረኞችን ከላይ ወደታች እያየ ነበር። አውቶቡሱ የያዘውን ይዞ አደባባዩን መዞር ሲጀምር ግን በሁላችንም ገጽታ ላይ ድንጋጤ መነበብ ጀመረ።
እኔ እንደሚመስለኝ የአውቶቡሱ የላይኛው አካል እንቅስቃሴ የሚዘወረው በእስፕሪንግ  ታግዞ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ መንገደኛው በተለመደው አካሄድ  በአንድ ስፍራ ላይ ፀንቶ መቀመጥ አይችልም። እንዲህ  መሆኑ ለአብዛኞቻችን ምቾት አልሰጠንም። ምሽት፣ ጨለማና ፍርሀት ተደማምረውም ጉዞውን አሳሳቢ ማድረጋቸው አልቀረም። አጋጣሚው በተለይ ለእንደኔ አይነቷ  ኮሽታና ከፍ ያለ ድምጽ ለሚያስበረግገው ሁሉ ከባድ የሚባል ነው።
እኛ ከታችኞቹ አናት ላይ ፊጥ ብለን እየተጓዝን መሆናችን ሳስበውና ከእነሱ የምንተያይበት አንዳችም ምክንያት እንደሌለ ሲገባኝ፣  በአፈጣጠሩ ጥበብ መደነቅ ጀመርኩ። ግን ይህ አድናቆቴ ጥቂት እንኳን ሳይቆይ ስፕሪንጉ መወዛወዝ ጀመረና ፍርሀቴ መልሶ ተቆጣጠረኝ። በዚህ መሀል  መለስ ብዬ የሌሎቹን ገጽታ ተመለከትኩ። ሁሉም  ከእኔ የባሱ  መስለው ታዩኝ። እንደውም አብዛኞቹ «ምነዋ እግሬን በሰበረው» ሳይሉ እንደማይቀሩ ገምቻለሁ። መቼም የፍርሃት ጉዳይ ሆኖ እንጂ ይህን ያህል ለህይወት የሚያሰጋ  አልነበረም። እኛ ለቴክኖሎጂው አዲስ መሆናችንና  ጉዞውን ደጋግመን አለመልመዳችን ጭምር ግራ ቢያጋባን አይፈረድም። እንግዲህ አንዴ ገብተናል። እዚህ ላይ  ‹‹ደፋርና ጭስ…››  ይሉት ተረት  ትርጉም የለውም።
አሁን በአጭር የከፍታ በረራ ላይ እንገኛለን። እውነትም በረራ። ሁሌም ከመሬት አንጋጠን ወደላይ  የምናያቸው የቀለበት መንገድ ድልድዮች ሳይቀሩ አሁን በተራቸው ዝቅ ብለው እያዩን ነው። ከስራችን የሚሯሯጡት ተሽከርካሪዎችም እምብዛም ጎልተው አይታዩም። ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን በፎቅ ላይ ለምንገኘው ብቻ እንጂ ለታችኞቹ ተጓዞች አይደለም።
ወይ ጉድ እናንተዬ! ለካንስ የፍርሀት መንገድ እንዲህ ይርቅ ኖሯል?። አውቶቡሱ ወዝወዝ ባለቁጥር ልቤ «ምንጥቅ» እንዳለች ነው። ፍሬን ለመያዝ ሲሞክር ደግሞ ይባስ ያስደነግጣል። ምን ይደረግ እንግዲህ!ደፋርና ጭስ አልተገናኙማ። እዚህ ላይ የጭሱን መውጫ ባላውቅም ደፋር ተብዬው ግን በቀላሉ የሚያዋጣው አይመስልም።
መቼም እኔም ሆንኩ ሌሎች ለዚህ ልማድ የመጀመሪያዎች እንደመሆናችን ብንደናገጥ አይገርምም። ወደፊት ግን ሁሉም ተለምዶና ተወዶ ከቴክኖሎጂው እንደምንወዳጅ  ዕምነቴ ነው። ያም ሆነ ይህ አሁን  የሁላችንም መውረጃ ደርሷል። የምድርና የፎቁ በሮች እኩል እንደተከፈቱ እኔ  በድፍረት በገባሁት  ጠባብ  ደረጃ  በፍጥነት ለመውረድ  ቸኩያለሁ። ከነበርኩበት ወጥቼ የውጩ ዝናብ እስኪቀበለኝም «ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም» በሚል ሳጉረመርም ነበር።

መልካምሥራ አፈወርቅ

Published in መዝናኛ

በእንግሊዝ በርሚንግሃም ከተማ ሲካሄድ በነበረው 17 ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ላይ የተሳተፈው ኢትዮጵያ አትሌቶች ልኡካን ቡድን ደማቅ አቀባበል ተደረገለት። ልኡካን ቡድኑ ትናንት በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ፤የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ርስቱ ይርዳው፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ክቡር ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ እና ከልዩ ልዩ ተቋማት ተወክለው የተገኙ የሥራ ኃላፊዎችና የሚዲያ ተቋማት ጋዜጠኞች ተገኝተዋል፡፡


የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት ሚኒስትር አቶ ርስቱ ይርዳው፤በቻምፒዮናው በተገኘው አኩሪ ውጤት ምስጋና እና የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። «ኮርታችሁ ያኮራችሁን አትሌቶቻችን ነገም እንደመንግሥት ከጎናችሁ ነን »ሲሉ አበረታተዋል።


የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ፤በተሳታፊ ብዛት ሌሎች አገራት የተሻሉ ሆነው ቢገኙም በጥቂት አትሌቶች በአምስት ሜዳልያዎች ማስመዝገብ መቻላችን ትልቅ ስኬት መሆኑን ተናግሯል።ይህ ቢሆንም ግን ከአትሌቶቻችን ገና ብዙ ይጠበቃል ፡፡ከዚህ በተሻለ ተሳትፎና ውጤት በዓለም አደባባይ ላይ ልንታይ ይገባናል »ብሏል።


ከየካቲት 22 እስከ 25 ቀን 2010 ዓ.ም በእንግሊዝ በርሚንግሃም ከተማ ሲካሄድ በነበረው 17ኛው የዓለም የቤት ውስጥ በቻምፒዮናው አምስት ወርቅ፤ ስድስት ብርና ሁለት ነሐስ አስመዝግባ በአንደኛነት ካጠናቀቀችው አሜሪካ ቀጥሎ ኢትዮጵያ አራት ወርቅና አንድ ብር በማስመዝገብ ከዓለም ሁለተኛ ከአፍሪካ ደግሞ ቀዳሚውን ደረጃ ይዛ ማጠናቀቋ ይታወቃል። ይህም በቻምፒዮናው ታሪክ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ 2008 ስፔን ቫሌንሺያ ካስመዘገበችው አራት ወርቅ፤ አንድ ብርና አንድ ነሐስ በመቀጠል በሁለተኛነት እንድትቀመጥ አድርጓታል።

ዳንኤል ዘነበ

Published in ስፖርት

በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ትልቅ ሚና አለው፡፡ አምራች ዜጋን በመፍጠር ግዙፍ የኢኮኖሚ ምንጭ መሆን እንደሚችል ይነገርለታል፡፡ በሰላማዊ እንቅስቃሴ ፍቅርን፣ መተሳሰብን፣ አንድነትንና መተጋገዝን በመስበክ ዲፕሎማሲያዊ ሥራን በማከናወን በፖለቲካው ዘርፍ እጁን የማስገባት አቅም አለው-ስፖርት፡፡
በዚህ ደረጃ ጠቀሜታ እንዳለው በሚነገርለት ስፖርት የሚፈለገውን ዘርፈ ብዙ ውጤት ለማግኘት የተቀናጀ ሥራ ግድ ይላል፡፡ ከመንግሥት ሠራተኛው እስከ ግሉ ዘርፍ፤ ከአርሶ አደሩ እስከ ባለሀብቱ ድረስ ቅብብሎሻዊ ድጋፍ መታከል ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ዕውን መሆን ደግሞ የሚመለከታቸው አካላት በንቃት ሊሳተፉና ሊሰሩ ይገባል፡፡
የስፖርት ማህበራት ራሳቸውን እንዲያጠናክሩ እንዲሁም ስፖርቱ ቀስ በቀስ ከመንግሥት ድጎማ እንዲላቀቅ በስፖርት ፖሊሲው ጭምር ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ይገልፃል፡፡ ሚኒስቴሩ የበጀት ዓመቱን የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ሲያቀርብ ይህንኑ እውነታ አስረድቷል፡፡
በሪፖርቱ እንደተመላከተውም በክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በኩል በተደረገ ገቢ የማሰባሰብ ሥራ 91 ሚሊዮን 480 ሺ 580 ብር ተሰብስቧል። የስፖርት ማህበራቱ በበኩላቸው 34 ሚሊዮን 048 ሺ 179 ብር አሰባስበዋል። ይህም የዕቅዱ 31 በመቶውን ብቻ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡ አፈፃፀሙ ኅብረተሰቡ ለስፖርት በተለያዩ ደረጃ እያደረገ ያለው የፋይናንስ፣ የቁሳቁስና ሌሎች የተሳትፎ ድጋፍ አነስተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡
የሐረሪ ክልል ስፖርት ኮሚሽን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጌታሁን መኩሪያ፤ የስፖርት ማህበራትን ከመንግሥት ድጎማ ውጪ በማድረግ ኅብረተሰቡ እንዲይዛቸው ማድረጉ የስፖርቱ ዘርፉን እድገት ያፋጥናል ይላሉ። ኅብረተሰቡ የገንዘብና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ የስፖርቱን የገንዘብ አቅም ማሳደግ እንደሚቻል ይገልፃሉ። የሀብት አሰባሰብ ለስፖርቱ ዕድገት ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ጠቁመው፣ እንደየልሎቹ ተጨባጭ ሁኔታ የየራሳቸው የሀብት ማሰባሰብ ዘዴ ይኖራቸዋል ብለዋል።
«እንደ ሐረሪ ክልል ወጣቱ በስፖርቱ ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ የመዘርጋት እንቅስቃሴ ይደረጋል» ያሉት አቶ ጌታሁን፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የሀብት ማሰባሰቢያ ሰነድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። በሐረሪ ክልልም ሰነዱን መሠረት በማድረግ በክልሉ የሚገኙትን ባለሀብቶች፣ አርሶ አደሮችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ እንቅስቃሴ መደረጉን ይናገራሉ። በክልሉ በኢንቨስትመንት ከተሰማራው ከተርኪ ኢንተርናሽ ናል ኮርፖሬሽን ለበርካታ ፕሮጀክቶች የትጥቅና የቁሳቁስ ድጋፎችን በመጠየቅ ድጋፍ መገኘቱን በማሳያነት ያቀርባሉ፡፡
በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የውጭ ድርጅቶች ለፕሮጀክቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ንድፈ ሃሳብ በማዘጋጀት ተሳትፏቸውን ለማሳደግ ሲሰራ መቆየቱንም አቶ ጌታሁን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ጅምር ሥራዎች እንዳሉ ጠቁመው፤ የክልሉ ነዋሪ በተለያዩ ደረጃዎች ለስፖርቱ ድጋፉን እንዲሰጥ የማድረጉ ተግባር የሚፈለገው ደረጃ ላይ አልደረሰም ብለዋል፡፡ ስለዚህ ያሉትን ውስን ተግባራት አስፍቶና አጠናክሮ መሄድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግዛቸው መኮንን የብስክሌት ስፖርትን በማሳያነት በመጥቀስ የሀብት አሰባሰብ ተግባሩ አስፈላጊ እንደሆነ ያመላክታሉ። «ብስክሌት ከሌሎች ስፖርቶች አንጻር ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ የስፖርት ዓይነት ነው። በርካታ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ይካሄዳሉ። ይሄንን ለማድረግ ደግሞ በርካታ ሀብት ያስፈልጋል። ከዚህ በተጓዳኝ የውድድር ብስክሌቶች ያስፈልጉታል። የውድድር ብስክሌቶች ደግሞ ዋጋቸው በጣም ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ተቀናጅቶ የመስራቱ ሁኔታ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም» ይላሉ። ይሁንና ጥረቱ ከአስፈላጊነቱ አኳያ ብዙ ይቀረዋል። ስለዚህ በቀጣይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያገነዝባሉ፡፡
የስፖርት ማህበራት ከመንግሥት ድጋፍ ውጪ በመሆን ሕዝባዊ አደረጃጀትን ተላብሰው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸውም ያነሳሉ። በፌዴሬሽኑ በኩል እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች መኖራቸውን ይገልፃሉ። ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ስፖርታዊ ውድድሮች በቋሚነት ስፖንሰር እንዲደረጉ እንደሚሰሩ አመላክተዋል።
ስፖርቱን ለማሳደግ ሀብት ማሰባሰብ ላይ ትኩረት ማድረግ ተገቢ መሆኑን ገልጸው የስፖርት ማህበራት አሁንም ከመንግሥት ድጎማ እና እጅ አልወጡም ይላሉ። ለዚህም ክልሎች፣ ፌዴሬሽኖችና የስፖርት ማህበራት በሀብት ማሰባሰብ ላይ ያደረጉት ጥረትና የሰጡት ትኩረት ከሚፈለገው በታች እንደሆነ ይጠቁማሉ። ፌዴሬሽኑ፣ ክልሎችና ባለድርሻዎች ይህንኑ ክፍተት እንደሚቀበሉት ያክላሉ፡፡
«ለስፖርቱ እድገትም ሆነ መጠናከር የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም» ያሉት ደግሞ የጋምቤላ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ታደለ ኢሬሶ ናቸው። ስፖርቱን የሚመራው አካል ኅብረተሰቡ የሚጠበቅበትን እንዲጫወት ዕድሉን ማመቻቸት እንደሚገባው ይገልፃሉ። በሚገነቡ የስፖርት መሠረተ ልማቶች ላይ ኅብረተሰቡ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ ማመቻቸት፣ ባለሀብቱ ክለቦችን በስፖንሰርነት እንዲይዝ መንቀሳቀስ፣ ክለቦች ሕዝባዊ መሠረት እንዲይዙ መስራት፤ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ለፕሮጀክቶች የትጥቅና ሌሎች ድጋፎችን ማድረግ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ከሚገለጽባቸው ጉዳዮች ውስጥ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ ከእነዚህ አንፃር እንደ ጋምቤላ ክልል የተደረገው እንቅስቃሴ በጣም ዝቅተኛ ነው ይላሉ።
አቶ ታደለ በማብራሪያቸው፤ በክልሉ በርካታ ኢንቨስተሮች በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ። እነዚህን ባለሀብቶች በክልሉ የሚደረጉ ውድድሮችን፣ ፕሮጀክቶችን፣ ክለቦችን እንዲይዙ፣ የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ በመለገስ እንዲያጠናክሩ የማድረግ ዕድሉ ሰፊ ነው። ይሁንና ይህንን አቅም በመጠቀም ረገድ ብዙ አልተሰራም፡፡
ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው ለጉዳዩ ቅድሚያ አለመስጠት ነው። ይህ ተሞክሮ በክልል ብቻም ሳይሆን በአገር አቀፍ ደረጃም ቢሆን ብዙም ትኩረት የተሰጠው አለመሆኑ በሌሎቹ ክልሎች በቀረበው ሪፖርት ላይ ተመላክቷል። ስለዚህ በሁሉም ደረጃ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ባይ ናቸው።
በስፖርቱ ዘርፍ የኅብረተሰቡን ተሳትፎ ለማሳደግ በክልሎች፣ በፌዴሬሽኖች ብሎም በስፖርት ማህበራት በኩል የተሰራው ሥራ ውስን መሆኑ ሁሉንም አስተያየት ሰጪዎች ያስማማ ጉዳይ ሆኗል፡፡ የስፖርት ማህበራትን ከመንግሥት እጅ በመረከብ ሕዝባዊ መሠረትን በመያዝ የገንዘብ አቅማቸውን እንዲያጠናክሩ በማድረግ ረገድም ጥረቱ በአነስተኛ የተግባር ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል። በክልሎችም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ሊሰሩና መሰራት ያለባቸው የቤት ሥራዎች በአስተያየቶቹ ተንፀባርቀዋል፡፡ የሐረሪ ክልሉ አቶ ጌተሁን በክልል ደረጃ ካለው ነባራዊ ሃቅ በመነሳት መሰራት ስለሚገባቸው ሊሰሩ የታሰቡ ሥራዎችን ይጠቁማሉ፡፡
«በአስመጪነትና በሌሎች ዘርፎች ተሰማርተው የሚገኙ በርካታ ባለሀብቶች በክልላችን ይገኛሉ። ይህንን አጋጣሚ መሠረት በማድረግ በስፖርት ዘርፍ እንዲሰማሩ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የታሰበ ቀጣይ ሥራ አለ። በሆቴል ኢንዱስትሪ የተሰማሩ ባለሀብቶች ሕዝባዊ መሠረት ያላቸውን ክለቦች ስፖንሰር እንዲያደርጉ፤ በስፖርቱ ዘርፍ የሚደረጉ የመሠረተ ልማት እንቅስቃሴዎችን በገንዘብ እንዲደግፉ ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው» ብለዋል፡፡ ሌሎች አካላትም በዚህ ላይ ትኩረት አድርገው መስራት እንዳለባቸው አቶ ጌታሁን ምክረሃሳባቸውን አቅርበዋል።
የጋምቤላ ክልሉ አቶ ታደለ በሌላ በኩል በክልሉ የሚገኙ ባለሀብቶች ሆቴሎችን ሲገነቡ በሆቴሉ ውስጥ ሊከናወኑ የሚችሉ ስፖርታዊ ጨዋታዎችን (ኢንዶርስ ጌም) ማስተናገድ በሚችሉበት መልኩ እንዲሆኑ ትኩረት መስጠት አለባቸው፡፡ ለዚህም ለባለሀብቶቹ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡ ከከተማ ልማት ጋር የተቀናጀ መመሪያ በማውጣት ተፈጻሚ እንዲሆኑ መስራት እንደሚገባ ይናገራሉ። በክልል ደረጃ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ክለቦች ቢቋቋሙ ካለው የብቃት እና የአቅም ሁኔታ ክልሉ በርካታ ስፖርተኞችን ማፍራት ይችላል፡፡
ይህ አቅም ደግሞ ከክልል ተሻግሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ውጤታማ ለመሆን እንደሚያግዝ እምነት አላቸው። በመሆኑም እነዚህን ጉዳዮች ታሳቢ ያደረጉ ተግባራትን ለማከናወን መታሰቡን ነው ምክትል ኃላፊው የገለጹት።
የብስክሌት ፌዴሬሽኑ አቶ ግዛቸው እንደ ሌሎቹ አስተያየት ሰጪዎች ሁሉ ስፖርቱን ለማሳደግ ኅብረተሰቡን በተለያዩ ደረጃዎች ያሳተፈ የሀብት ማሰባሰብ ሥራ ከመስራት አኳያ የሚፈለገው ደረጃ ላይ አልደረሰም ይላሉ። ከዚህ ክፍተት በመነሳትም እንደ ብስክሌት ፌዴሬሽን በክልል ከሚገኙ ፌዴሬሽኖችና ክለቦች ጋር በመሆን በቀጣይ ሰፊ ሥራዎችን ለመስራት መታሰቡን ነግረውናል።
በአጠቃላይ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ረገድ የክልሎችም ሆነ የስፖርት ማህበራት እንቅስቃሴ ጥያቄ ውስጥ ያስገባም ሆኖ ተገኝቷል። የሚኒስቴሩን ሪፖርት መሠረት በማድረግም ቀጣይ ምን ሊሰራ እንዲገባ እና ያለው እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል ክልሎች እና የስፖርት ማህበራት ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል። ይህ እውነታ የስፖርት ማህበራት አሁንም ከመንግሥት ድጎማ እና እጅ እንዳይወጡ አድርጓቸዋል። ኅብረተሰቡ ለስፖርቱ የገንዘብም ሆነ ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ የዘርፉን የገንዘብ አቅም ለማሳደግ የተሰራው ሥራ በክልልና በፌዴራል ደረጃ የሚፈለገው ደረጃ ላይ አልደረሰም፡፡ በቀጣይ ሁሉም አካላት ለሀብት ማሰባሰብ ሥራው ልዩ ትኩረት በመስጠት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጥሪ ቀርቧል፡፡

ዳንኤል ዘነበ

Published in ስፖርት

ወጣት ነው። ዝምታ የሚያበዛ፤ ከሰው የማይገናኝ ብቸኛ። ይህን የሚያውቁ ብዙዎች ሊቀርቡት አይፈልጉም። እንዲህ ሊያደርጉ ቢሞክሩ እንኳን አብሮት የኖረው ክፉ ስያሜና የማንነት መገለጫ ምልክቱ ከማንም አያስጠጋውም። በአካባቢው መቼ እንደመጣ፣ ወዴት እንደሚሄድና መቼ እንደሚመለስ የሚያውቅም ሆነ የሚጠይቅ የለም። ስለውሎ አዳሩ የሚጨነቅና የሚያስብም ተፈልጎ አይገኝም ።
ዘወትር ከላዩ የማይለየውን ኮፍያ እንዳጠለቀ ከተማውን ሲያካልል ይውላል። በደረሰበት ስፍራ ሁሉ ስለ እሱ እንግድነትና ፀጉረ ልውጥነት የሚያሳስበው ተመልካች የለም። መነሻና መድረሻው፣ ውሎና አዳሩ እግሩ ከጣለው ስፍራ ነው። ምቹ መኝታ፣ በቂ ምግብና ዕንቅልፍ፣ ልብስና መኖሪያ በእሱ ዘንድ ትርጉም የላቸውም። ከጉስቁልናው ጀርባ አብሮት የሚዞረው «ዕብድ» ይሉት ስያሜ ከሌሎች አራርቆ በራሱ ዓለም ቢያኖረው ብቸኝነትን መርጧል።
ብቸኛው ወጣት ዘወትር ከማይጠፋበት የአየር ጤናው ካራ አካባቢ የሚያውቁት ሁሉ በኮፍያው ምልክት ይለዩታል። በአጋጣሚ የቀረባቸውና ድንገት ሲያልፉ የተጠጉት ቢኖሩ ግን ዳግም ከጥጉ ድርሽ አይሉም። ገና በሩቁ የማያስቀርበው ክፉ ሽታ ተጨማሪ መለያው ሆኗል። ማንም ግን ይህ ስለ ለምን ሆነ? ሲል የተጨነቀ አልነበረም። ባለ ኮፍያው ወጣትም አብሮት ካለው ስያሜና ሰው ከማያስቀርብ መጥፎ ጠረኑ ጋር በመንከራተት ጊዜያትን አሳልፏል።
አንድ ቀን ይህ ወጣት ከአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከመጡና በአካባቢው ከደረሱ ሰዎች አይን ውስጥ ገባ። አመጣጣቸው እሱን መሰል ወገኖችን ከወደቁበት ማንሳትና ወደህክምና ማድረስ ነበር። ወጣቱ የአዕምሮ ህመምተኛ መሆኑ ይታወቃል። እሰከዛሬ ግን የት ነህ ብሎ የፈለገውም ሆነ የጠየቀው የለም። ዛሬ እሱን ፈላጊ መኖሩና «አለንህ» የሚል ዘመድ መምጣቱ ብዙዎችን አስገርሟል። ከወደቀበት የሚያነሳው፣ ሰው መሆኑን የሚያስታውሰው አጋር ዘመድ አግኝቷልና።
በስፍራው የደረሱት ባለሙያዎች ወጣቱን በፍቅር ቀረቡት። እያግባቡና እያጫወቱም ለጉዞ ወደተዘጋጀው መኪና አስገቡት። ይህ ሁሉ ሲሆን ምንም ቅሬታና ተቃውሞ አላሳያቸውም። በመኪናው ውስጥ ሌሎች እሱን መሰል ወገኖች ተቀምጠዋል። ሁሉም የሚገኙበት የህመም ደረጃ የተለያየ ቢሆንም ለጉዞ ያስቸገረና «እምቢኝ» ሲል የታገለ ግን እምብዛም አልነበረም።
ባለኮፍያው ወጣት ከሌሎች ጋር ተቀላቀለ። ወንበር ተሰጥቶትም ስፍራውን ያዘ። እሱ በተቀመጠ አፍታ ግን መኪናው እጅግ ከባድ በሚባል ክፉ ሽታ ታወደ። ሁሌም ቢሆን ለባለሙያዎቹ የአዕምሮ ህመምተኞችን የቆሸሸ ልብስ ማየትና የማይመች ሽታን ማስተናገድ አዲስ አይደለም። አሁን ለአፍንጫቸው የሚደርስው ሽታ ግን ከተለመደው የተለየና እጅግ ከባድ የሚባል ሆነ። በግራ መጋባት ስሜት የቆዩት የቡድኑ አባላት መድረሻቸውን በአካባቢው ከሚገኝ ጤና ጣቢያ እንዳደረጉ ቅድሚያ የሰጡት የህሙማኑን ገላ ማጠብ፣ ልብሳቸውን መቀየርና ፀጉርና ጥፍራቸውን መቁረጥ ነበር።
ባለኮፍያው ወጣት ልክ እንደሌሎቹ የዕድሉ ተካፋይ ይሆን ዘንድ ተራው ደረሰው። ባለሙያዎቹ የቆሸሸ ልብሱን አውልቀው ሲያጥቡትና ፀጉሩን ሲቆርጡለት ከቆየበት ያልተመቸ ገጽታው እንደሚላቀቅ ገምተዋል። ይህን አስቀድሞ ያወቀው ወጣት ግን የታሰበው ሁሉ እንዳይሆን አሻፈረኝ ሲል መጮህ ጀመረ። ልብሱን እንዳይነኩበትና ወደ ኮፍያው ቀርበው ፀጉሩን እንዳይቆርጡበትም በእጅጉ መታገል ያዘ።
እንደምንም አግባብተው በእጃቸው ለማስገባት ሞከሩ። ጨኸቱና መታገሉ አስቸጋሪ ቢሆንም ቀስ ብለው ኮፍያውን አነሱት። ወዲያው ግን የነበረው ከባድ ሽታ በእጥፍ ጨመረ። በተያያዘው ፀጉሩ ስር የሚወርደው ፈሳሽም አንገቱን እያራሰ ወደ አካሉ ተዳረሰ። ይህ ሲሆን የወጣቱ ስቃይ በረታ። እውነታውን ቀርበው ለሚያዩ ሁሉም ከባድ የሚባል ሀዘንን አጫረ። በተቆጣጠረው ፀጉር ስር የሚታየው የወጣቱ ጭንቅላት ለሁለት የተከፈለ ይመስላል። በተለይም በታችኛው ክፍል የሚታየው ቅርጽ በጥልቀት የተከረከረ ስለመሆኑ ይለያል።
ይህን ያስተዋሉ የህክምና ባለሙያዎች ሚስጥሩን ለማወቅ ይበልጥ ቀርበው መረመሩ። የምርመራቸው ውጤት ልባቸውን ቢሰብረውም ከአንድ እውነታ አደረሳቸው። በወጣቱ ጭንቅላት ውስጥ ጠልቆ የሚታየው ሚስጥር ለዓመታት ጠብቆ የታሰረ፣ በደምና በቁስል ብዛት ዝጎ የቆየ ሽቦ ሆኖ ተገኘ። እሱ ይህን መቼ እንዳደረገው አይታወቅም። ለበርካታ ጊዜያት አብሮት በኖረው ስቃይ ግን ሲንገላታ ቆይቷል። ከአዕምሮ ህመሙ ባሻገር የደረሰበት አካላዊ ጉዳት የከፋ ቢሆንም ከመገለል በተለየ ምን ሆንክ ብሎ የጠየቀው ግን አልነበረም። ማንም!።
ሌላ አሳዛኝ ባለታሪክ፡፡ ጥግ ላይ ከአንዲት ትንሽ የውሻ ቤት ውስጥ የተዘጋባቸው አዛውንት ወድቀዋል። እሳቸው በሚኖሩበት ኮልፌ ቀራንዮ አካባቢ የሚገኙ ሰዎችም ለዓመታት ትንፋሻቸውን እያዳመጡ የሚበሉት፣ የሚጠጡትን ሲጥሉላቸው ኖረዋል። እሳቸው የሚኖሩትም ሆነ የሚፀዳዱት ውለው በሚያድሩበት ስፍራ በመሆኑ ስለማንነታቸው የሚያውቅና መልክና ቁመናቸውን ለይቶ የሚናገር የለም።
በዚህ ስፍራ የአዕምሮ ህሙማኑን የሚጎበኙትና የሚያነሱት ባለሙያዎች ድንገት ሲደርሱ አዛውንቱ በራቸውን በላያቸው ዘግተው መኖራቸውን እንደቀጠሉ ነበር። ለዓመታት የተዘጋችውን ትንሽዬዋን የውሻ ቤት ከፍተው ሲገቡ ግን የተመለከቱት እውነታ እጅግ አስደንጋጭ ነበር።
ሰውዬው ዕድሚያቸው ገፍቷል። አካላቸውም ደክሟል። የጸሐይ ብርሀን አይተው ስለማያውቁም ለእሳቸው የደጁን አየር መቀላቀል አዳጋች የሚባል ነው። ከሁሉም በላይ ግን ለዓመታት በአንድ ስፍራ ታጥፈው የመቀመጣቸው ችግር አካላቸው እንዳይታዘዝና ከወገባቸው በታች እንዳይንቀሳቀሱ ማድረጉ ያሳዝናል።
በአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ደጅይጥኑ ሙላው በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በተደረገው የአዕምሮ ህሙማንን የማሰባሰብ ዘመቻ ተሳታፊ ነበረች። ሁሌም እነዚያን ጊዜያት መለስ ብላ ስታስታውስ ከልቧ ታዝናለች። በተለይ በየስፍራው ወድቀው የሚገኙ በርካታ የአዕምሮ ህሙማን ቤተሰብና ወገን እያላቸው እንደ አሮጌ ዕቃ የመወርወራቸው እውነት ያስቆጫታል።
የአዕምሮ ህመም በህክምና የሚድን መሆኑ ቢታወቅም በህብረተሰቡ ዘንድ የኖረው የተሳሳተ አመለካከት ከችግሩ በቀላሉ ለመላቀቅ እንዳይቻል ምክንያት ሆኗል። በዚህ አስቸጋሪ የህመም መንገድ የሚያልፉ ወገኖች ጥቂት ባይባሉም በተለይ ደግሞ ችግሩ ሲከሰት በሴቶች ላይ የሚኖረው ጫና የበረታ እንደሚሆን ትገልፃለች።
ሴቶች ከህመማቸው ጋር ጎዳና ላይ ሲወድቁ የሚደፈሩበትና ልጅ የሚወልዱበት አጋጣሚዎች ይበረክታሉ። ይህም ሲሆን ስለወለዷቸው ልጆች የሚያውቁበት አጋጣሚ ላይኖር ይችላል። ደጅ ይጥኑ ለዚህ ማሳያ ቤላ አካባቢ ያገኟትን የልጅ እናት ታስታውሳለች። ይህቺ ሴት በጎዳና ህይወቷ ከወለደችው ልጅ ጋር ብትኖርም እሱን ይዛ ከመጎተት ባለፈ ለይታ አታውቀውም። ይህን ያስተዋሉ አንዲት ሴት ህፃኑን ለመንከባከብ ከእናቲቱ ነጥለው ሲወስዱም ስለመኖር መጥፋቱ የምታውቀው ነገር አልነበረም።
ከቆይታ በኋላ በህክምና ተረድታ የአዕምሮዋ ጤና ሲመለስ ያሳለፈችውን ህይወት ለማስታወስ አልተቸገረችም። ልጇን ከነበረበት ሲያመጡላትም አቅፋ የተቀበለችው በጣም ልብን በሚነካ ሀዘንና በመሪር ለቅሶ ነበር።
ደጅ ይጥኑ ይህቺን ሴት ጨምሮ ከተለያዩ ስፍራዎች የተነሱ የአዕምሮ ህሙማን በሆስፒታሉ ታክመው መዳናቸውንና በተሻለ የጤንነት ደረጃ ላይ መገኘታቸውን ትናገራለች። ሌሎች በርካቶችን ከነበሩበት ችግር ለማላቀቅ ግን ህብረተሰቡ ህመሙ አይድንም ከሚለው ተለምዷዊ የተሳሳተ አመለካከት መራቅ እንደሚገባው የምትመክረው በአጽንኦት ነው።
በከተማዋ የተለያዩ ጥጎች ወድቀው ከተረሱና ከተገለሉት መሀል አብዛኛዎቹን የሚቀርባቸው የለም። ስለ እነሱ መብላትና መጠጣት፣ በሰላም ውሎ ማደርና መነሳትም ማንም ግድ አይሰጠውም። እነዚህ ወገናች ከየት ይምጡ፣ ወደ የት ይሂዱ፣ ይሙቱ አልያም ይጥፉ ነገሬ የሚላቸውም አይኖርም። ይልቁኑም በእጅጉ ያደፈ ልብሳቸውንና አላስቀርብ የሚል ክፉ ሽታቸውን የሚጠየፈው ይበረክታል። ከዓመት እስከ ዓመት፣ ክረምት ከበጋ የሚፈራረቅባቸውን ብርድና ጸሐይ አስተውሎ ከንፈር ከመምጠጥ ሌላ ለእነዚህ ዜጎች «ቤት ለእንግዳ» የሚልም አይገኝም።
ብዙዎቹ በቤተሰባቸው መሀል በእግር ብረት እንደታሰሩ፣ ቤት እንደተዘጋባቸውና እንደተገለሉ አመታትን ያሳልፋሉ። እነሱ እንናገር ቢሉ እንኳን ፈጽሞ የሚያደምጣቸውና የሚያምናቸው አይኖርም። ከሰው ሊቀርቡ ቢሞክሩም ከሩቁ አይቶ የሚሸሻቸው ይበዛል። «ዕብድ» የሚለው የወል መጠሪያ ዳር ላለው ተመልካች ሁሉ ዘወትር አስደንጋጭና ከባድ የሚባል ስሜት አለው። ይህ እውነታም የአዕምሮ ህመም መዳን ሲችል እንዲባባስና ህሙማኑን በችግሩ ውስጥ ዓመታትን እንዲያልፉ አስገድዷል።
በአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአዕምሮ ሀኪሙ ዶክተር ክብሮም ሀይሌ የአዕምሮ ህመም ተላላፊ ካልሆኑና በርካቶችን እየጎዱ ከሚገኙ በሽታዎች መሀል ዋነኛው መሆኑን ይናገራሉ። አስራ አንድ ከመቶ የሚሆነው የህመም ጫና መነሻውም የአዕምሮ ህመም ስለመሆኑ ይገልፃሉ። ያም ሆኖ ግን እጅግ ብሶባቸዋል ከሚባሉ የአዕምሮ ህሙማን መሀል ህክምናውን የሚያገኙት ከአስር ከመቶ በታች የሚሆኑት ብቻ ናቸው።
አሳሳቢውን የአዕምሮ ህመም ችግር ለመቅረፍ የህብረተሰቡን የተዛባ አመለካከት ለመቀየር በባለሙያዎች የተጠናከረ ሰፊ እንቅስቃሴ ማደረግ እንደሚገባ ዶክተር ክብሮም ይናገራሉ፡፡ ይህንን ለማሳካትም አገልግሎቱን የማስፋት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። እ..ኤ .አ በ2020 የአዕምሮ ጤና ህክምና በማንኛውም የጤና ተቋም እንዲሰጥ የማድረግን ኃላፊነትን ለመወጣት የተለያዩ መመሪያዎች በመዘጋጀት ላይ ናቸው። በዚህ ሂደትም ማንኛውም የጤና ባለሙያ ህክምናውን እንዲሰጥ የማድረግ ሁኔታዎች ይመቻቻሉ።
በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ እጅግ አሳሳቢ የሆነውን የአዕምሮ ጤና ችግር ለመታደግ የሚያስችልና በዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ተቀባይነት ያለው ዕቅድና ስትራቴጂ ተነድፏል። ይህ በመሆኑም ያልተማከለና የተቀናጀ የህክምና ሂደቱ ተግባራዊ ሆኖ እየተሰራበት ይገኛል። በተለያዩ ክፍለ ከተሞችም በርካታ የጤና ባለሙያዎች ሰልጥነው ህክምናውን በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
የአዕምሮ ህመም በማን ላይ መቼ ሊከሰት እንደሚችል አይታወቀም። ትላንት ጤነኛ የነበረ ዛሬ ጨርቁን ጥሎና አቅሉን ስቶ ሲታይም አብዛኞቻችን ከንፈር ከመምጠጥ በዘለለ ለመፍትሄው ስንጣጣር አይስተዋልም። ህመሙ እንደማንኛውም በሽታ ታክሞ የሚድንና መፍትሄ ያለው መሆኑን ግን ልብ ልንል ይገባል። የአዕምሮ ጤና ችግር የሁላችንም ጉዳይ ነውና።

 

Published in ማህበራዊ

የአገሪቱ ኢኮኖሚ ክፉኛ እየተጎዳ ይገኛል፡፡ ዜጎች በአገሪቱ በተፈጠረው መልካም አጋጣሚ ሰርተው መጠቀምና አገሪቱ ከምታመነጨው ምርት መጠቀም የሚችሉበት ዕድል እየጠበበ ነው፡፡ በምትኩም ኢኮኖሚውን የሚያቀጭጭ የፀረ ድህነት ትግሉንም የሚያዳክም እንቅስቃሴ መከሰት ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ ይህንን ሁኔታ በተለመደው የህግ ሥርዓት መቀልበስ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡
ሂደቱን ማስተካከል የሚቻለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመተግበር መሆኑ ታምኖበት አዋጁ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም ተደንግጓል፡፡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም ፀድቋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የህግ አስከባሪዎች በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ተሰማርተው ተልዕኮአቸውን እየተወጡ ይገኛል፡፡
አዋጁን መሰረት በማድረግም የአዋጁን ዝርዝር ህጎች ለማስፈጸም የሚያግዙ ዝርዝር ደንብና መመሪያ ማውጣት እንደሚቻል በህጉ ተመልክቷል፡፡ በዚሁ መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት በዝርዝር ለመፈጸም እንዲያስችለው የአፈፃፀም መመሪያ አውጥቷል፡፡
ዜጎች በመመሪያው ዙሪያ ግንዛቤ እንዲ ጨብጡ፣ ሁከትና ብጥብጥ በተከሰተባቸውና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በከንቱ ቅስቀሳና ፕሮፖጋንዳ ተታልለው የሁከትና ብጥብጡ አካል የሚሆኑ ሰዎች ከእኩይ ተግባራቸው እንዲቆጠቡና ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊነት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተመልክቷል፡፡ የሁከትና የብጥብጥ ኃይሎች፣ ጠንሳሽና አራማጅ የሆኑ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ሲሉ ከትናንት በስቲያ በመመሪያው ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት የፌዴራል ጠቅላይ ዋና ዐቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ አመልክተዋል፡፡
አዋጁን ለማስፈጸም ህጉ ተልዕኮ የሰጠው ለአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስቱ የተሰጠውን ኃላፊነት ለመፈጸም እንዲችል መመሪያ ቁጥር አንድ 2010 ዓ.ም ሁለት ክፍሎችን የያዘ 24 አንቀጾች የተቀመጡበት መመሪያ አውጥቶ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ገብቷል፡፡
መመሪያው በክፍል አንድ የተከለከሉ ተግባራትን የያዘ ሲሆን ይህ በመላው አገሪቱ የተከለከሉትን ተግባራትና ኮምንድ ፖስቱ በሚወስናቸው የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ብቻ የታጠሩና የተከለከሉ ተግባራት ናቸው፡፡
1. በመላው አገሪቱ የሚተገበሩ ክልከላዎች
1.1 ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር መፈጸም
ይህ በመላ አገሪቱ መመሪያው ከከለከላቸው ተግባራት ተርታ ይመደባል፡፡ በወንጀል ሕጉ ከአንቀጽ 238 እስከ 260 በተደነገገው መሰረት ድርጊቱን ፈጽሞ መገኘት ወንጀል ነው፡፡ በወንጀል ድርጊቱ የተሳተፈም ከሦስት ዓመት እስከ 20 ዓመት በህዝብ ደህንነት ኑሮ ላይ ከፍተኛ ቀውስ ካስከተለ ደግሞ እስከ ዕድሜ ልክ እንደሚቀጣ በወንጀል ህጉ የተደነገገው ይተገበራል፡፡
1.2 የህዝቦችን አንድነትና መቻቻልን የሚጎዳ ተግባር መፈፀም
የህዝቦችን አንድነትና መቻቻልን የሚጎዳ ተግባር መፈጸም በመመሪያው ክልክል ነው፡፡ ማንኛውም ህብረተሰብ በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢዎች ተዘዋውሮ የመኖር፣ ሀብት የማፍራት ሕገ መንግሥታዊ መብቱ አይገደብም፡፡ ማንነትን፣ ፆታን፣ ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖትና የፖለቲካ አመለካከትን መሰረት ያደረገ በህይወት፣ በአካልና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ በፍፁም የተከለከለ ነው፡፡
1.3 ከአሸባሪ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ማድረግ እና መደገፍ
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጁትን ኦነግ፣ ኦብነግ፣ ግንቦት ሰባትና መሰል ሽብርተኛ ድርጅቶችን መደገፍ በህግ ያስጠይቃል፡፡ ከእነዚህ አካላት አመራሮቹና አባላት ጋር ግንኙነት መፍጠር ለእነርሱም ድጋፍ ማድረግ ሕገ ወጥነት ነው፡፡ ጽሁፋቸውን መያዝ፣ ማሰራጨት፣ አርማቸውን ይዞ መገኘት፣ በግልጽ የህዝብ አደባባይ ላይ ቆሞ ሽያጭ ማካሄድ በሕግ ያስቀጣል፡፡
1.4 የትራንስፖርት እንስቃሴን ማወክ
የህዝብ ትራንስፖርት እንቅስቃሴን ማወክ ወይም መገደብ፣ የባቡር ትራንስፖርት እንቅስቃሴን መገደብ፣ በትራንስፖርት መሰረተ ልማቶቹ ላይ ጉዳት ማድረስ፣ መንገዶችን በማንኛውም መልኩ በመዝጋት እንቅስቃሴን መገደብን መመሪያው ከልክሏል፡፡ በዛቻና በማስፈራራት፣ ሰላማዊ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን ማወክ፣ ታሪፍ መጨመር፣ ከሥራ ስምሪት ውጭ መሆን በፍፁም የተከለከሉ ናቸው፡፡
1.5 የህዝብ አገልግሎትን ማስተጓጎል፣ ማቋረጥ እና መዝጋት
የህዝብን አገልግሎት ማስተጓጎል፣ መዝጋትና ማቋረጥ በመመሪያው ተከልክለዋል፡፡ ህዝቡ የሚጠቀምባቸው የአገልግሎት ቦታዎችን መዝጋትና ማቋረጥ ክልክል ነው፡፡ በተለይም የንግድ ፍቃድ የወጣባቸው የንግድ ተቋማትን ማቋረጥና መዝጋት የተከለከለ ተግባር ነው፡፡ የመንግሥት ተቋማት እንዲዘጉና እንዲስተጓጎሉ ምርትና አገልግሎታቸው እንዲቋረጥ ማድረግንም መመሪያው ከልክሏል፡፡ በመንግሥትና በግል አገልግሎት መስጫ ተቋማት የተሰማራ ሠራተኛ ያለ በቂ ምክንያት ከሥራ መጥፋት፣ ከሥራ መቅረትና ሥራ ማቆም አይችልም፡፡
1.6 በመሰረት ልማትና ተቋማት ላይ ጉዳት ማድረስ
በህዝብና በመንግሥት ተቋማት በተዘረጉ መሰረተ ልማቶች ላይ ምንም አይነት ጉዳት ማድረስ የተከለከለ ነው፡፡ በግል ንብረት ላይ ጉዳት ማድረስና ዘረፋ መፈጸም በህግ ያስቀጣል፡፡ 1.7 የህግ አስከባሪዎችን ሥራ ማወክ
የህግ አስከባሪን ስምሪትና ተልዕኮ ማወክ እንዲሁም በህግ አስከባሪ አካላት ላይ ጥቃት መፈጸም አይቻልም፡፡ ሠላምና ፀጥታ ለማስከበር የሚያስተላልፏቸውን ትዕዛዞችን አለማስተላለፍ የተከለከለ ነው፡፡ የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ሲባል ለአደጋ አጋላጭ ናቸው በተባሉ ቦታዎችና አካባቢዎች ፍተሻ በሚያደርጉበት ጊዜ ለፍተሻ አለመተባበር በፍፁም አይቻልም፡፡ ኬላዎችን ጥሶ ማለፍ ክልክል ነው፡፡ ታራሚዎችን ለማስለቀቅ ወይም እንዲያመልጡ ማድረግ የተከለከለ ነው፡፡
1.8 ያልተፈቀደ ሰልፍ እና የአደባባይ ስብሰባ ማድረግ
ኮማንድ ፖስቱ አውቆ አስፈላጊነቱን አምኖበት ያልፈቀደው ሰልፍና የአደባባይ ስብሰባ ማድረግ አይቻልም፡፡ ይህንን አድርጎ መገኘትና ከኮማንድ ፖስቱ እውቅና ውጭ የሚፈጸሙ ሰልፎችና የአደባባይ ስብሰባዎች ፈጽሞ ተከልክለዋል፡፡
1.9 በትምህርት ተቋማት አድማ ማድረግ
ከዚህ ቀደም በትምህርት ተቋማት ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት ደርሷል፡፡ የሁከትና የብጥብጡ ኢላማዎች ከሆኑት መካከል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ሌሎች ተቋማት እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ተቋማቱ ከዚህ አይነቱ ብጥብጥና ሁከት የጸዱ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ትግበራ ወቅት የሚሰራ ተግባር ነው፡፡ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያውክ አድማ ማድረግ አይቻልም፡፡ ተቋማቱ እንዲዘጉ የሚደረግ እንቅስቃሴ አይፈቀድም፡፡ በመሰረተ ልማቶቹም ጉዳት ማድረስ በመመሪያው ክልክል ሆኖ ተቀምጧል፡፡
1.10 በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች አድማ ማድረግ
በስፖርት ደጋፊዎች መካከል ባልተገባ ፉክክር ሁከትና ግርግር እንዲሁም የአድማ ማነሳሳት ተስተውሏል፡፡ በመሆኑም ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጭ በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላት ካሉ የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድ በመመሪያው ተቀምጧል፡፡
1.11 ሁከትና ብጥብጥ የሚያነሳሳ ቅስቀሳ እና ግንኙነት መፍጠር
ቅስቀሳው ሁከትና ብጥብጥ የሚያስነሳ፣ በህዝቦች መካከል መቃቃርንና መጠራጠርን የሚፈጥር ትዕይንት ማሳየት አድማና ህገ ወጥ ተግባርን የሚያበረታታ ተግባር የተከለከለ ነው፡፡ መልዕክትን በማናቸውም መንገዶች ቀርፆ ማስተላለፍ ያስቀጣል፡፡ ፈቃድ ሳይኖር ማንኛውንም ህትመት ወደ አገር ውስጥ ማስገባት ወይንም በአገር ውስጥ የተዘጋጁ ጽሁፎችን ወደ ውጭ አገር መላክ የተከለከለ ነው፡፡ ይዘታቸው ሁከትና ብጥብጥ የሚፈጥሩ መልዕክቶችን በማንኛውም መንገድ ማስተላለፍም ወንጀል ነው፡፡
1.12 የመሰረታዊ ሸቀጦችን ዝውውር ማወክ
ህብረተሰቡ ለዕለት ኑሮው መደጎሚያ የሚያስፈልገውን የሸቀጥ ዝውውር በምንም መንገድ ማገድ፣ ማወክና ማስተጓጎል አይቻልም፡፡ 13. ባህላዊ፣ ህዝባዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ብሄራዊ በዓላትን ማወክ
ከበዓሉ ዓላማ ጋር የማይያያዝ የፖለቲካ አጀንዳ አስገብቶ መቀስቀስ አይቻልም፡፡ ከበዓሉ ዓላማ ባፈነገጠ መንገድ መፈክሮችን ማሰማትና እንቅስቃሴ ማድረግ አይፈቀድም፡፡ በበዓላቱ ላይ የኃይል ድርጊት መፈጸም፣ ዛቻና ማስፈራራት፣ መጠራጠርና መቃቃርን የሚፈጥር ቅስቀሳና እንቅስቃሴ ማድረግ በወንጀል ያስጠይቃል፡፡
1.14. በገበያ፣ ሃይማኖታዊ ተቋማት፣ በበዓላት እና ሕዝብ በተሰበሰበበት ስፍራ የጦር መሳሪያ ይዞ መግባት
ማንኛውም የጦር መሳሪያ ወይም ስለት ያላቸው መሳሪያዎችና እሳት የሚያስነሱ ነገሮች ወደተወሰኑ ቦታዎች በየትኛውም የአገሪቱ ክልሎች ይዞ መግባት፣ የገበያ እንቅስቃሴ በሚደርግበት ቦታ፣ ማናቸውም ህዝብ በሚሰበሰቡባቸው ቦታዎች ላይ፣ ሃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት ላይ ይዞ መግባት የተከለከለ ነው፡፡
15. ትጥቅን በሦስተኛ እጅ እንዲገባ ማድረግ
የህግ አስካባሪ ኣካልም ይሁን ህጋዊ የትጥቅ ፍቃድ ያለው ሰው መሳሪያውን ለሦስተኛ ወገን አሳልፎ መስጠት የተከለከለ ነው፡፡ መሳሪያ እስከተሰጠው ድረስ መሳሪያው በራሱ እጅ መሆን አለበት፡፡
1.16. የህዝብን ሠላምና ፀጥታ ለማደፍረስ የገንዘብ፣ የቁሳቁስ እና ሌሎች ድጋፎችን ማድረግና መተባበር
የህዝብን ሠላምና ፀጥታ ለማደፍረስ የሚውል ድጋፍ ማድረግ አይቻልም፡፡ የድጋፉ ዋነኛ አላማ የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ ማድፍረስ እስከዋለ ድረስ በማንኛውም መንገድ የተከለከለ ነው፡፡ የድጋፉ አይነት በገንዘብ፣ በቁሳቁስ ወይም በሌሎች መንገድ ሆኖ የህዝብን ሠላምና ፀጥታ አደጋ ውስጥ የሚጥል እስከሆነ ድረስ ድረስ በህግ የተከለከለ ነው፡፡ ወንጀል የፈፀሙ አካላትን ከለላና መጠለያ መስጠት፣ ድጋፍ ማድረግ መደለያ በመስጠት ማበረታታትና የመሳሰሉት ሁኔታዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተከለከሉ ናቸው፡፡ ይህን አድርጎ የተገኘም በህግ ተጠያቂ እንደሚሆን በመመሪያው ተቀምጧል፡፡
1.17. በፀጥታ ጉዳይ ላይ መግለጫ መስጠት
በተለያዩ ወቅቶች በተለያዩ ጉዳዮች የፌዴራል አካላት፣ የክልል አካላት መግለጫ ይሰጣሉ፡፡ በአስቸኳይ አዋጁ ትግበራ ጊዜም በልማት፣ በዴሞክራሲና በመልካም አስተዳደር ጉዳይ መግለጫ መስጠት ይችላሉ፡፡ ሆኖም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት በጸጥታ ጉዳይ ላይ የፌዴራል መንግሥትም ይሁን የክልል ኃላፊዎች ለህዝብ ይፋ የሆነ መግለጫ መስጠት አይችሉም፡፡ በፀጥታ ጉዳይ መግለጫ መስጠት ያለበት የፌዴራል ኮማንድ ፖስቱ ወይንም በተዋረድ ያሉ የኮማንድ ፖስት አካላት መግለጫ እንዲሰጡ መመሪያ ከተሰጣቸው በፀጥታ ጉዳይ መግለጫ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ክልልም ሆኑ የፌደራል አካላት ይህንን የማክብር ግዴታ አለባቸው፡፡ ይህን ተላልፎ መገኘትም ያስጠይቃል፡፡ በልማት፣ በመልካም አስተዳደር እና በዴሞክራሲ አጀንዳ እንዳይሰጡ የሚከለክል ነገር በመመሪያው የለም፡፡
1.18ኛ. የአዋጁንና አዋጁን ተከትሎ የወጡ ህጎችን ትግባራዊነትን ማክበር፡፡
የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ከወጣ በኋላ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ራሱን የቻለ ደንብ ወጥቷል፡፡ ድንቡን ተከትሎ መመሪያ ወጥቷል፡፡ የአዋጁን ደንቦችና መመሪያዎች መቃወም የተከለከለ ነው፡፡ መቃወም ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ ማሰራጨትም በደንቡና መመሪያ መሰረት ክልክል ነው፡፡ የደንቡንና መመሪያውን ይዘት በአግባቡና በሥርዓቱ ማሰራጭት እንደተጠበቀ ሆኖ ይህን አዛብቶ ማስተላለፍ ያስጠይቃል፡፡
በክፍል አንድ ንኡስ ክፍል እንድ ላይ ከአንቀፅ አንድ እስከ አንቀፅ አስራ ስምንት የተቀመጡት በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የተከለከሉ ተግባራት ናቸው፡፡ ስለዚህ በሁሉም ክልሎች ውስጥ የሚገኙ የአገሪቱ ህዝቦች እነዚህን ሁኔታዎች አውቀው ለተግባራዊነታቸው ምላሽ መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡ በሁከትና ብጥብጡ ሰለባ የሚሆኑ ወገኖች ከእንደዚህ አይነት ድርጊት ራሳቸውን መቆጠብና ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊነት መሥራት አለባቸው፡፡ የሁከትና ብጥብጥ ኃይሎችም ከድርጊታቸው መቆጠብ ይኖርባቸዋል፡፡
2 በተወሰኑ የአገሪቱ ክፍሎች የሚተገበሩ ክልከላዎች
2.1 የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ
የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት ይፋ በሚያደርጋቸው ስፍራዎች የትኛውንም የጦር መሳሪያ፣ ስለት ወይንም እሳት የሚያስነሱ ነገሮች ይዞ መንቀሳቀስ አይፈቀድም፡፡
2.2 የሰዓት እላፊ ገደብ
የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት ይፋ በሚያደርጋቸው ስፍራዎች የሰዓት እላፊ ገደብ ይጣላል፡፡ በዚህ የሰዓት እላፊ ገደብ ውስጥ የሚካተቱት፤ ሰፋፊ የኢኮኖሚ አውታሮች ያሉባቸው ቦታዎች ሆነው ትልልቅ ፋብሪካዎችንና መሰረተ ልማት አውታሮች፣ ሰፋፊ እርሻዎች ያሉባቸውና ኢንቨስትመንት የሚካሄድባቸው ቦታዎችን ያጠቃልላል፡፡ የመኖሪያና የሥራ ቦታዎች ላይ ኮማንድ ፖስቱ የሰዓት ዕላፊ ገድብ ሊጥል ይችላል፡፡ ኮማንድ ፖስቱ በሚወስነው ጊዜ ከተፈቀደው ሰዓት ውጭ ለመንቀሳቀስ ከተፈቀደለት ውጭ መንቀሳቀስ ፈፅሞ የተከለከለ ነው፡፡ የሰዓት ዕላፊ ገደቡ የኮማንድ ፖስቱ በሚያሳውቀው መሰረት ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ እገዳውንና ክልከላውን ተላልፎ የተገኘ ሰው የጥበቃ ወይም የህግ አስከባሪ አካላት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ ስልጣኑ የተሰጣቸው መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ይህንን ሁኔታ አውቆ ከዚህ አይነት ድርጊት ራስን መቆጥብ ተገቢ ነው፡፡
2.3. ሁከትና አዳጋን ለማስቆምና አደጋን ለመከላከል የሚደረግ
እንቅስቃሴዎችን ማወክ፤ በተከለከሉ ቦታዎች ሁለት አይነት እርምጃዎች ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡
1ኛ ሠላምና ፀጥታን ለማደፍረስ ይችላሉ ተብለው የሚጠረጠሩ ሰዎች ወይም ቡድኖች ካሉ አደጋ ሊያደርሱ ስለሚችሉ ባሉበት ቦታ ሳይንቃሳቀሱ በአንድ ኣካባቢ እንዲቆዩ የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስቱ ሊያዝ ይችላል፡፡
2ኛ ለጉዳት ተጋላጭ ናቸው ተብለው የሚታሰቡ የህብረተሰብ ክፍሎችና ቡድኖች በአንድ ቦታ ላይ እንዲቆዩ ወይም እንዲወጡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስቱ ትዛዝ ካስተላለፈ ያንን የማስፈፀም ግዴታ ይኖራል፡፡ ለምሳሌ ኮማንድ ፖስቱ ሴቶች፣ ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን በአንድ በተወሰነ ቦታ ላይ ቢቆዩ አደጋ ይደርስባቸዋል ብሎ ካመነ ወደ ሌላ ቦታ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ይችላል፡፡
አልያም ከዚህ ቦታ ቢንቀሳቀሱ ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል ብሎ ካመነ እዛው ቆይተው የደህንነት ጥበቃ እንዲደረግላቸው ያዛል፡፡ ይህንን ተላልፎ መገኘት ተገቢነት እንደሌለው መመሪያው ያስቀምጣል፡፡ ይህ እርምጃ በሚወሰድበት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስቱ በሚገልፀው መረጃ መሰረት አክብሮ መገኘት ተገቢ ነው፡፡ እነዚህ ሦስት አንቀፆች በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ኮማንድ ፖስቱ ገልፆ በሚያወጣቸው ቦታዎች አካባቢ ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡
2ኛ ለአካባቢው ደህንነት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ወደተዘጋ መንገድ ማንም እንዳይገባ ኮማንድ ፖስቱ የሰጠውን እግድ ወይም ክልከላ መተላለፍ ክልክል ነው፡፡ ይህም ኮማንድ ፖስቱ በየጊዜው ለህዝብ ይፋ በሚያደርገው ላይ ተመስርቶ ተግባራዊ ይሆናል፡፡
3. የመተባበር እና የማሳወቅ ግዴታ
3. 1 የቤትና የተሽከርካሪ አከራዮች
የተከራይን አካል ማንነት መዝግቦ በግልፅ መያዝ፣ በፅሁፍ የሰፈረውን መረጃ በ24 ሰዓት ውስጥ ለፖሊስ ማሳወቅ፣ ተከራዩ የውጭ አገር ዜጋ ከሆነ የተከራዩን ፓስፖርት እና የኪራይ ውል ለፖሊስ የማቅረብ ግዴታ አለባቸው።
በከተሞች በማንኛውም ቦታ በኪራይ መልክ የሚገለገሉትን ቤት፣ ተሽከርካሪ ወይም ሌሎች ነገሮችን የሚያከራይ ግለስብ የተከራዩን ማንነት በግልፅ መያዝ አለበት፡፡ ይህ ሳይፈጸም ቀርቶ አደጋ ቢከስት ግለሰቡ ከተጠያቂነት አይድንም፡፡ በተለይም ተከራዩ የውጭ አገር ዜጋ ከሆነ የግለሰቡን ፓስፖርት ቅጂና የኪራዩን ውል በማያያዝ ለፖሊስ ጣቢያ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡
3.2 መረጃ የመስጠት ግዴታ
ማንኛውም የፌዴራልና የክልል ተቋም መረጃ በተጠየቀበት ጊዜ ለህግ አስከባሪ አካል መረጃ የመስጠት ግዴታ አለበት። ማንኛውም ተቋም በተጠየቀበት ጊዜ ለህግ አስከባሪ አካል መረጃ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡
3.3 ማንኛውም ሰው የኮማንድ ፖስቱን ውሳኔ የማክበር እና የመተግበር ግዴታ አለበት፡፡
ከላይ የተገለፁት ክልከላዎች ተላልፈው ወይንም ተጥሰው ቢገኙ ስለሚወሰዱ ርምጃዎች
4. እርምጃዎች
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፎ መገኘት እርምጃዎችን ያስወስዳል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንቀጽ 16 የተመለከተውን መተባበርና ግዴታዎችን ተላልፎ መገኘት እርምጃ ለመውሰድ ሁለተኛው ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጣስ ወይም ከዚህ ጋር ተያያዝና ተደራራቢ የሆኑ የወንጀል ድርጊቶችን በፈፀመና በድርጊቱ በተጠረጠረ ሰው ላይ አዋጁ እርምጃ መውሰድ ይቻላል፡፡ ዲፕሎማቶች መብታቸው አይጣስም፡፡
የሚወሰዱ እርምጃዎችም ፦
ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ በቁጥጥር ስር ማዋል፡ በቁጥጥር ስር የሚውሉ ሰዎችን ኮማንድ ፖስቱ በወሰነው ቦታ እንዲቆዩ ይደረጋል፤ ማንኛውም ስፍራ እና አካል ላይ በማንኛውም ሰዓት ብርበራ ማድረግ፤ የተዘረፉ ንብረቶችን አጣርቶ ለባለቤቶቹ መመለስ፤ በትምህርት ተቋማት ረብሻ የሚፈጥሩ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ፤ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማዘዝ ይችላል።
5. የኃይል አጠቃቀም
የህግ አስከባሪ አካላት እና የጥበቃ ኃይሎች የራሳቸውን ደህንነት መጠበቅ ይችላሉ። የዜጎችን ደህንነት እና የኢንቨስትመንት ተቋማትን የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው። ይህንን ግዴታቸውን ለመወጣት ተመጣጣኝ ኃይል መጠቀም እንደሚችሉም በመመሪያው ተደንግጓል።

በጋዜጣው ሪፖርተሮች

Published in ፖለቲካ

ከሕዝብ ካለው የመልማት ፍላጎት አንፃር በየጊዜው የተለያዩ የልማት ጥያቄዎች ለመንግሥት ይቀርባል። ሆኖም መንግሥት ካለው ውስን ሀብትና ብልሹ አሠራር ሳቢያ አንዱን ጥያቄ ሳይመልስ ሌላ ጥያቄ ይከተላል፡፡ በዚህም የህዝብን ፍላጎት በሚፈለገው ደረጃ ማርካት አልተቻለም። እነዚህ በየጊዜው የሚነሱ የልማት ጥያቄዎች ሳይመለሱ ውለው ሲያድሩ የቅሬታና የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ እየሆኑ ናቸው።
ለዚህ ነው መንግሥት በረጅም ጊዜ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል አዲስ የመንግሥትና የግል አጋራነት አሠራር ጀምሯል።
በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የመንግሥትና የግል አጋርነት ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር ተሾመ ታፈሰ፤ ቶሎ ትርፍ የማያስገኙ፣ ለአገር ልማት ከፍተኛ ጥቅም ያላቸው እና የህዝብን የአገልግሎት ጥያቄዎች ሊመልሱ የሚችሉ መሰረተ ልማቶችን በግልና በመንግሥት አጋርነት የሚከናወኑ መሆኑን ያብራራሉ።
ዶክተሩ፤ እንደሚሉት በግልና በመንግሥት ትብብር የሚለሙ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ፋይናንስ የሚያስፈልጋቸው፣ ወጫቸው በረጅም ጊዜ የሚከፍሉና ለህዝብ ሰፊ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው። መንግሥት ዝርዝር ጥናት አድርጎ ቶሎ ሊሠራቸው የማይችላቸውን የልማት መርሀ ግብሮች ጨረታ አውጥቶ ለግል አልሚዎች ይሰጣል። መንግሥት የልማት መርሀ ግብሮቹ በጥራት፣ በተያዘላቸው ጊዜ እና በውሉ መሰረት መከናወናቸውን ይቆጣጠራል። የልማት መርሀ ግብሮቹ ተሠርተው ከተጠናቀቁ በኋላ ከመሰረተ ልማት ተገልጋዮቹ ገንዘቡን በመሰብሰብ በተገባው ውል መሰረት ለአልሚው ክፍያ ያከናወናል። ይህ አሠራር በደቡብ ኮሪያ፣ በቻይና፣ በጃፓን፣ በእንግሊዝና በሌሎች በርካታ አገራት ተሞክሮ አወንታዊ ውጤት አምጥቷል። ከዚህ ተሞክሮ በመነሳትም በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣውን የህዝብ የልማት ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል አሠራር መሆኑን ነው የሚናገሩት።
የዓለም ባንክ የንፋስ ኃይል ገምጋሚና የቦታ መረጣ ባለሙያ ሚስተር ራሁል ኪችሉ፤ ኢትዮጵያ የመንግሥትና የግል አጋርነት ተግባራዊ ለማድርግ መጀመሯ የአገሪቱን ሁለተናዊ ዕድገት ፍጥነት ይጨምራል። ከዓለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ለመሥራት ያስችላል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የግሉ ዘርፍ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲያለሙ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ይህም መንግሥት፣ ህዝብንና የግሉን ዘርፍ ተጠቃሚ ያደርጋል። ይህን አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ የመንግሥት ውሳኔ ማስተላለፉን አድንቀዋል።
ባለሙያው የመንግሥት ውሳኔ የሚደነቅ ቢሆንም ሥራው በርካታ አካላትን የሚያካትትና ውስብስብ በመሆኑ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነው። በጥልቅ ጥናት ላይ መመስረት አለበት። የመንግሥትና የግል አጋርነት ተሳታፊዎችም የሚያደርጉት እያንዳንዷ ስምምነት ግልጽና ተጠያቂነት ሊኖረው ይገባል። የፋይናንስ አቅርቦት፣ የቴክኒክ ሥራዎች አካሄድ፣ የአካባቢና የማህበራዊ ጥናት፣ የመሬት አቅርቦት፣ የቴከኖሎጂ አጠቃቀም እና ሌሎች በሥራው ላይ የሚከናወኑ ጉዳዮች ሁሉ መተማመን ላይ ተደርሶና ውል ታስሮ መገባት አለበት። ይህንን መንገድ መከተል ከተቻለ ሁሉም አካል የሚያተርፍበት ይሆናል። እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዲጊ አገራት ስልቱ በጣም አዋጭ እንደሆነም ሳይጠቅሱ አላለፉም።
የዴኒማርክ ኢነርጂ ኤጀንሲ የኃይል ባለሙያ ሚስተር አንድሪ ኢስዶሪ፤ "የንፋስ ኃይል ልማት ፍኖተ ካርታ" በሚል ባቀረቡት ጽሁፍ በዓለም ላይ በርካታ አገራት ፊታቸውን ወደ ንፋስ ኃይል እያዞሩ ነው። እኤአ በ2015 በአገራቸው ዲንማርክም ካለው የኃይል ፍጆታ የንፋስ ኃይል 42 በመቶ ድርሻ እንዳለው አመልክተው ልማቱን ለማካሄድም የመንግሥትና የግል አጋርነት ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ከግሉ ሴክተር ጋር ጠንካራ አጋርነት በመፍጠር ሁሉንም አካል ተጠቃሚ ለማደርግ በቅድሚያ መሠራት ያለባቸው የቤት ሥራዎች እንዳሉም ባለሙያው ምክረ ሀሳቦች አሏቸው። የረጅም ጊዜ ዕቅድ ማዘጋጀት። ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድርግ ግልጽ ፖሊሲና ስልት መንደፍ። ግልጽና ተግባራዊ የሚሆኑ የህግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት፤ ተቋም ማቋቋምና ብቁ የሰው ኃይል መመደብና ዘመናዊ አሠራሮችን መዘርጋት ይገባል ባይ ናቸው። በአጠቃላይ የመንግሥትና የግሉ አጋርነት ለረጅም ጊዜ የሚቆይ በመሆኑ ከፍተኛ መተማመንና የሚሰሩትም ሥራዎች ከጥናታቸው እስከ አተገባበራቸው ጥራታቸውን የጠበቁ መሆን ይገባቸዋል ብለዋል።
የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሽ በቀለ፤ በበኩላቸው በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨረሻ አገሪቱ ከውሃ፣ ከንፋስ፣ ከእንፋሎት ኃይልና ከፀሐይ 17 ሺ ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት እየሠራች ነው። ይህም በአፍሪካ የኃይል ማዕከል በመሆን ከራሷ አልፋ ሌሎች አገሮች ኃይል በማቅርብ የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም ላይ እያደረሰ ያለውን ችግር የሚታደግ መሆኑን አብራርተዋል።
የተያዙትን እቅዶች ተግባራዊ ለማድርግ መንግሥት እያደረገው ካለው ጥረት በተጨማሪም በልማቱ ላይ የግሉ ዘርፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀር ተሳታፊ መሆን አለባቸው። የግሉ ዘርፍም ተሳታፊ ለማድረግም የመንግሥትና የግል አጋርነት ተግባራዊ ማድርግ የሚያስችል አዋጅ ጸድቋል። መንግሥት ከሚሠራው የታዳሽ ኃይል ልማት በተጨማሪ የግሉ ሴክተር፣ ብድር የሚሰጡ ዓለም አቀፍ ተቋማትና መንግሥታት ከፍተኛ ሚና ይጨዋታሉ። ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የኃይል ሀብትም ለራሷና ለጎረቤቶቿ ኃይል የማቅረቡን እቅድ ለማሳካት ያስችላል ብለዋል።
መንግሥት ይህን ተግባራዊ ለማድርግ በአጋርነት ሊሠሩ የሚችሉ ልማቶችን በአገር ውስጥና በውጭ አገር ባለሙያዎች ጭምር አስጠንቷል። በጥናቱ የሀብት ማግኛ ዘዴዎችን፣ በአጋርነት የሚለሙ ዘርፎችን፣ ማዋቅሩንና ሌሎች አሠራሮችን ተግባራዊ የሚያደርጉ ሥርዓቶች የመዘርጋት ሥራም እየተከናወነ ነው። የዘርፉ ፍኖተ ካርታ በመዘጋጀት ላይ ሲሆን ይህን መሰረት ተደርጎም ወደ ሥራ እንደሚገባም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የስትራቴጂና የኢንቨስትመንት ኃላፊው አቶ መኩሪያ ለማ፤ በኃይል ዘርፉ አጋርነቱን ተግባራዊ ለማድርግ አሠራሮች ተዘርግተዋል። ከንፋስ፣ ከውሃ፣ ከእንፋሎትና ከፀሐይ ኃይል የኤሌክትሪክ ኃይል ለማምረት በተለያዩ አካባቢዎች የአዋጭነት ጥናት ለማድረግ፤ በአካባቢና በማህበረሰብ ላይ የሚያደርስውን ጉዳትና የማካካሻና መንገዶችን የመለየት፤ የመሬት አጠቃቀም ጥናት ማድረግ፣ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማቅረብና የሕግ የማማከር አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋቱንም አብራርተዋል።
የግል ዘርፍ የተሰጠውን ሥራ በሚሠራበት ጊዜ የቴክኒክ ሥራዎችን ለመቆጣጠር፤ በሥራ ሂደት የሚገጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታትና አገሪቱ ያላትን የኃይል አማራጭ ወደ ጥቅም ለመለወጥ በሚደረገው ጥረት በተቀረፀው ፖሊስና ስትራቴጂ መሰረት ተግባራዊ ለማድርግ ተቋማቸው ዝግጁ መሆኑን አብራርተዋል።
የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የመንግሥትና የግል አጋርነት ዳይሬክተሩ ዶክተር ተሾመ በበኩላቸው እንደገለፁት በአገሪቱ አድማሱ እየሰፋ የመጣውን የመልማት ፍላጎት ለማርካት የግል አልሚዎች እንዲሳተፉ ይደረጋል፡፡ ይህም በቀላሉና በአጭር ጊዜ አገልግሎቱን ለህዝብ መስጠት የሚያስችል ነው። አሠራሩም የሕግ ማዕቀፍ ተዘርግቶለታል።
አጋርነቱ ወደ ሥራ ለማስገባት ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በኃይል አቅርቦት፣ በትራንስፖርት እና በተለያዩ ዘርፎች 40 ፕሮጀክቶች እየተጠኑ ናቸው። ጥናቱ ሲጠናቀቅ ፕሮጀክቶቹ ከአገሪቱ የልማትና ርዕይ ጋር የሚሄዱ መሆናቸው ሲረጋገጥና መንግሥት በራሱ አቅም የማይሰራቸው ከሆኑ የግል አለሚዎች እንዲሳተፉባቸው ጨረታ ይወጣል። መንግሥትም በተገቢው ጥራት መሠራታቸውን በመቆጣጠር ከተጠናቀቁ በኋላ ከአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ገንዘብ በመሰበሰብም ለአልሚዎቹ ክፍያውን ያከናውናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተመራጭ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መደራሻ መሆኗና፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን መገንባቷ፣ የአዲስ አበባ -ጅቡቲ የባቡር መሰመር መዘርጋቱ፣ ባለፉት 14 ተከታታይ ዓመታት 11 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት መመዝገቡና የተረጋጋ የኢኮኖሚ ዕድገት መኖሩ ለኢንቨስትመቱ ፍሰት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
እንዲሁም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በህዝብ ብዛት ሁለተኛ ደረጃን መያዟ በርካታ የመሰረተ ልማት ፍላጎት የተፈጠረባት አገር ያደርጋታል። በመሆኑም የአጋርነት ስልቱ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስና የአገሪቱን ዕድገትም ለማፋጠን ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።

አጎናፍር ገዛኸኝ 

Published in ኢኮኖሚ

እኤአ በ2015 የፀጥታው ምክር ቤት አባላት አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ እንዲሁም ጀርመን፣ ከኢራን ጋር የደረሱትን ሁሉን አቀፍ የኒውክለር ስምምነት ፍኖተ-ካርታ (ሮድማፕ) በሙሉ ድምጽ የማጽደቃቸው ዜና ተሰማ። በወቅቱም የኢራንን የኒውክለር ማበልፀጊያ ሂደት ቢያንስ ለቀጣይ አስራ አምስት ዓመታት ለመግታት የተነደፈው ፍኖተ-ካርታ ከአብዛኛው የዓለም ዓቀፍ ሕብረተሰብ ድጋፍ ሲቸረው የተወሰኑ አገሮች ተቃውሞቸውን እና ጥርጣሬያቸውን አንጸባርቀ ዋል። የጥርጣሬ ስሜትን ከአንጸባረቁት አገራት መካከል እሥራኤል ግንባር ቀደም ሆነች። በተለይም ደግሞ ስምምነቱን ከፈጸሙት አገራት ውስጥ አሜሪካ መኖሯ ለእሥራኤል ከምንም በላይ ያልተጠበቀ እና ዱብዳ ጭምር ነበር። ይሄንኑ ተከትሎ በወቅቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታናሁ በኩል «ኢራን ሂዝቦላን ታስታጥቃለች፣ የሶሪያን መንግሥት ትደግፋለች፣ በኢራቅ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ እጇ አለበት፤ አገሪቱ እስላማዊ ሪፕብሊክ ሆና እየቀጠለች ባለችበት ሁኔታ በጸጥታው ምክር ቤት ተጥሎ የነበረውን ማዕቀብ ማንሳት በዓለም ላይ ታሪካዊ ስህተት መፈጸም ነው፤ ለእሥራኤል የፀጥታና ደህንነት ካብኔያቸው «አሜሪካና እሥራኤል መውደም አለባቸው የሚል ጥሪ ለሕዝባቸው እያሰሙ ከእነሱ ጋር የሚደረግ አንዳችም ስምምነት አይኖርም»፤ በማለት የተላለፈውን ውሳኔ ላይ ጸኑ ተቃውሞዋን አሰማች። የኢራንን የኒውክለር ማበልፀጊያ ሂደትን አመድ ማድረግ የሚችል ጠንካራ ማዕቀብ ማድረግ እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጸንኦት ሰጥተው ለዓለም መንግሥታት ድምፃቸውን አሰሙ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእሥራኤል የቅርብ አጋር እንደሆነች የሚትታወቀውን አሜሪካን በጊዜው ፕሬዚዳንት የነበሩትን ባራክ ሁሴን ኦባማን ለማነጋገር ተደጋጋሚ ጉዞን ወደ አሜሪካ አድርገዋል። አሜሪካ እና እሥራኤል ይውደሙ፤ ይጥፉ የሚሉ መፈክሮች ከወደ ኢራን በተደጋጋሚ መሰማታቸውን አስምረውበት ይናገራሉ። ኢራን የኒውክሌር መሳሪያ ባለቤት ከሆነች የጥቃት ኢላማ የምታደርገው እሥራኤልን እና አሜሪካ ላይ እንደሚሆን ባራክ ኦባማን ሲጎተጉቱ ቆይተዋል። በወቅቱ የነበረ ምላሽ ባይኖርም። ለዘመናት አጋርነቷን ያሳየችው አሜሪካ በኦባማ ጊዜ ግን ፊቷን አዞረችባቸው። ነገር ግን በኦባማ የሥልጣን ቆይታ ወቅት ጆሮ እና ትኩረት የተነፈገው የቤንጃሚኒ ኔታናሁ ጩኸት፤ በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዘንድ ግን ትኩረት ማግኘቱን የዘገበው ሮይተርስ ነው።
ዶናልድ ትራም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በመሆን ወደ ነጩ ቤት ከገቡ ማግስት ጀምሮ ለኔታናሁ የጸሐይ ብርሃን ፈንጥቆላቸዋል። የቅርብ ክስተት ከሆነው የእየሩሣሌም የእሥራኤል ዋና ከተማነት እውቅና መስጠት ጀምሮ ትራምፕ ከኢራን ኒኩለር ስምምነት ራስን ማግለል ጨምሮ ከእሥራኤል ጎን መቆማቸውን ያሳዩበት ነው፡፡
ቤንጃሚን ኒታናሁ ትናንት በነጩ ቤተመንግ ሥት በመገኘት ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ሰኞ ዕለት ውይይት ማድረግ መጀመራቸው ተሰምቷል። ይሄንኑ ተከትሎ ኔታናሁ ባለፉት ጊዜያት ከአሜሪካ ያጡትን ትኩረት ዳግም መልሰው የሚጨብጡበት አጋጣሚ መሆኑን የዘገበው ዘ ሚድል ኢስት ሞኒተር ነው።
ዘገባው እንዳሰፈረው፤ የሁለቱ አገራት መሪዎች የተባበሩት መንግሥታት የኢራን መንግሥት የኒውክሌር ማብለያ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ ያስቀመጠውን እገዳ ላይ ማሻሻያ እንዲያደርግ፤ ተጨማሪ እገዳዎችን እንዲያስቀምጥ ስለሚቻልበት ሁኔታ ይወያያሉ። በተጨማሪም ኢራን በሶሪያ ውስጥ እያደረገች ያለችውን እንቅስቃሴ በምን መልኩ መመከት ይገባል የሚሉ ጉዳዮች ትልቅ ትኩረት የሚሰጣቸው መሆኑን የአሜሪካ እና የእሥራኤል ባለሥልጣናት አስታውቀዋል ።
ይሄንኑ ተከትሎም በኢራን የኒውክሌር መሣሪያ ዙሪያ የተደረሰውን ስምምነት አሜሪካ ለመጣስ ዳር ዳር እያለች ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሁለቱ አገራት ውይይት በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ብሎም የፀጥታው ምክር ቤት አባላት እንዳልጣማቸው ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተነገሩ ነው። በተቃራኒው ደግሞ ስምምነቱን ከጀምሩ ሲቃወሙ ለነበሩት ለእሥራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቤንያሚን ኔታናሁ ትልቅ የፖለቲካ ትርፍ እንደሆነም ነው የዘገበው።
ሮይተርስ ባወጣው ዘገባ ደግሞ፤ በዚህ ሳምንት የተባበሩት መንግሥታት ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተገኙት የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ «በኢራን የኒውክሌር ባለቤትነት ላይ በህብረቱ የተደረገው ስምምነት ላይ ማሻሻያዎች እና የጊዜ ገደቡም ሊራዘም ይገባዋል።» ማለታቸው ተከትሎ ከእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር የተጀመረው ውይይት አሜሪካ ከስምምነቱ ውጭ የሆነ እርምጃ ልትወስድ እንደመትችል ጠቋሚ መሆኑን ዘገባው አመላክቷል። ፕሬዚዳንቱ በወቅቱ ሕብረቱ ቴራን ዳግም ወደ ጠረጴዛ በመምጣት በጉዳዩ ላይ እንድትነጋገር ግፊት ማሳደር አለበት ማለታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን አሜሪካ ከስምምነቱ ራሷን በማግለል እንደ አገር በጉዳዩ ላይ የምትንቀሳቀስ መሆኑን መናገራቸውን ዋቤ በማድረግ ይሄንኑ ሃሳብ አጠናክሮ ሮይተርስ ጽፏል።
የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፌደራሪክ ሞርኒኒ ይሄንኑ ተከትሎ፤ ስምምነቱን መተው ወይም እንደገና መተዋወቅ አልፈለጉም። «የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እየሠራ ያለውን እና የሚያስረግጥ ስምምነትን መሰረዝ አይችሉም። «ይህ አንድ የኑክሌር ፕሮግራም እና የተከላካይ ጣልቃ ገብነት የከለከለ ስምምነት ነው። ያንን እናስታውስ፤» በማለት ተናግረዋል።
የዶናልድ ትራምፕ ንግግርን ተከትሎም የኢራኑ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሮሃኒ « እኛ ዛሬ ለማወቅ የቻልነው አሜሪካ ስምምነቱን ለማቆም ሰበብ እየፈለገች መሆኑን ነው። የተዘጋውን ጉዳይ ዳግም ማንሳት አስፈላጊም አይደለም» ሲሉ መናገራቸውን በዘገባው ይዞ የወጣው ደግሞ አልጀዚራ ነው። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ‹‹አሜሪካ በኒኩሌር ጉዳይ ላይ ከኢራን መንግሥት ጋር ህጋዊ ስምምነቶችን መፈጸሟ ጊዜን ከማባከን ውጭ ፋይዳ የለውም የሚል አቋም አላቸው። ከዚህም በተጓዳኝ በኦባማ የፕሬዚዳንትነት ወቅት ከአውሮፓ ሕብረት አባላቱ ጋር ከተደረሰው ስምምነት ውጭ መጓዝ የመታሰቡን አገሪቱን ቃል አባይ የሚያስብል እንደሆነ መናገራቸውን ይሄው ዘገባ አስነብቧል።
የኢራኑ ፕሬዚዳንት እንደገለፁት፤ አገሪቱ ዳግም ስለዚህ ነገር ለማውራትም ለመደራደር ፍላጎት እንደሌላት ሃሳቡን ቅቡል እንዳልሆነም አስታውቀዋል። ነገር ግን አሜሪካ ሕብረቱ የደረሰበትን ስምምነት ጥሳ ከወጣች ግን ኢራን የዩራኒየም ማበልፀግ ተግባሯን ዳግም የምትጀምር ይሆናል ሲሉ መናገራቸውን ዋቤ ያደረገው አልጀዚራ፤ የትራምፕ አካሄድ መካከለኛው ምሥራቅ ላይ ያለውን የተዳፈነ የሠላም እንቅስቃሴ ዳግም እንዲጋጋም የሚያደርግ ሊሆን እንደሚችል ጽፏል።
ሮይተርስ በሌላ ዘገባው ደግሞ፤ ሕብረቱ በኢራን ጉዳይ ላይ የደረሱበት ስምምነት በአባል አገራቱ ባለሥልጣናት ዘንድ ጠንካራ ድጋፍ ነው ያለው። አሜሪካ ከሌሎች የሕብረቱ አባል አገራት ጋር መግባባት መቻሉን ግን ጥያቄ ውስጥ የሚገባ መሆኑ ነው ያነሳው። በተለይ ደግሞ ከሩሲያና ቻይና እና እንዲሁም ከእነዚህ አገራት ደጋፊ ከሆኑ አገራት በኩል የሚኖረው ምላሽ መልካም መሆኑ የማይጠበቅ ነው። ይህ መሆን ካልቻለ ስምምነቱ እንዲሻሻል ጥያቄ ከማቅረብ በተጓዳኝ ከስምምነቱ ውጭ የሆነ እንቅስቃሴ ለማድረግ እስከመገደድ የምትደርስ መሆኑን ዶናልድ ትራምፕ ማስታወቃቸውን ዘገባው አስታውሷል። ስለዚህ አሜሪካ በግሏ እንቅስቃሴ ማድረግ አገሪቱን ትልቅ ጫና ውስጥ የሚከት እንደሆነ በዘገባው ሰፍሯል።
የአባል አገራቱ ድጋፍ በዚህ መልኩ ልታጣ ትችላለች ይባል እንጂ በተቃራኒው ደግሞ ከአሜሪካ ጎን የሚቆሙ አባላት መኖራቸውን ዘገባው አንስቷል። የትራምፕን ንግግርን ተከትሎ በስብሰባው ላይ አንዳንድ የሕብረቱ አባል አገራት ታላላቅ ባለሥልጣናት ልብ ማሸፈት እንደቻለ ጠቅሷል። የኢራንን የኒውክሌር እንቅስቃሴ በምን ደረጃ ላይ መሆኑን ለማወቅም ለየት ያለ መከታተያ ስልት ሊኖር እንደሚገባ በማመን፤ የመከታተያ ስምምነት ቢደረግ ለመደራደር ፍላጎት እንዳላቸው ያስታወቁ መሆናቸውን ነው የዘገበው።
የሕብረቱን አባላት ሙሉ ድጋፍ ሳያገኝም ሳያጣ፤ ከወደ እሥራኤል መገኘቱ ሌላ የፖለቲካ ትኩሳት ይዞ የመጣ ጉዳይ ሆኖ ቀርቧል ያለው ሚድል ኢስት ሞኒተር ነው። በዘገባው እንዳሰፈረው፤ ዶናልድ ትራምፕ በእሥራኤል ጉዟቸው በሚኖረው ቆይታ የኢራን የኒውክሌር ባለቤትነት ጉዳይ ላይ የሚመክሩ መሆኑ ታውቋል። በዛሬው ዕለት ከእሥራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታኒያሁ ጋር ውይይታቸውን ያደርጋሉ። የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሕብረት አባል አገራቱ በኢራን ጉዳይ ላይ የተደረሰውን ስምምነት እንዲሻሻል ካልተደረገ የራሴን መንገድ መርጣለው ሲሉ የተናገሩትን ቃል ለመፈጸም መንገድ መጀመራቸውን የሚያሳይ መሆኑን ጽፏል። ይሄንኑ ተከትሎ ለወትሮም ሠላም ነግሶበት የማያውቀው መካከለኛው ምሥራቅ ወደ ሌላ የጦርነት ምዕራፍ የሚያሸጋግርም ጭምር ነው ሲል ዘገባውን ሀሳቡን ቋጭቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤንያሚን ኔታኒያሁ በጉቦና በማጭበርበር የክስ ሂደት ላይ ቢሆኑም አሁንም ግን የእሥራኤልን ህልውና ለማስጠበቅ ተፍ ተፍ ማለታቸውን ቀጥሏል። ከዚህም በተጓዳኝ ደግሞ በኦባማ ጊዜ የዞረባቸውን የአሜሪካን ፊት በዶናልድ ትራምፕ ዘመን እየተመለሰ መሆኑን ማሳያ መሆኑን ከተለያየ ወገኖች እየተነሳ ይገኛል። ለዚህም ባለፉት ጊዜያት የፀጥታው ምክር ቤት አባላት አሜሪካን ጨምሮ በኢራን የኒውክሌር ጉዳይ ላይ ያስተላለፈው ውሣኔ ኔታናሁን እንቅልፍ የነሳቸው ጉዳይ ነበር። እኚህ ጠቅላይ ሚኒስትር ከዚህ የሥጋት ደጃፍ የመገኘታቸው ዕውነታ ግን፤ ከእሥራኤል ደህንነት በላይ በአገራቸው ውስጥ የነበራቸውን የፖለቲካ ተቀባይነት በከፍተኛ ሁኔታ እየተሸረሸረ መምጣቱ መሆኑን በወቅቱ በስፋት ሲነገር ቆየቷል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የኢራን የኒውክሌር ስምምነት፣ ኦባማ በኔታናሁ ላይ የተቀዳጁት ዲፕሎማሲያው ድል ተደርጎም ተነግሯል። በዚህ መንገድ ሲብጠለጠሉ የነበሩ ኔታኒያሁ በዶናልድ ትራምፕ ጊዜ ሥጋታቸው እንዲሻር በማድረግ አዲስ ምዕራፍ የሚያስ ጀምራቸው እንደሚሆን ከተለያዩ አቅጣጫዎች መሰማቱ ቀጥሏል።

ዳንኤል ዘነበ  

Published in ዓለም አቀፍ
Wednesday, 07 March 2018 16:51

ለነገ የማይሆን ዛሬ

ዛሬ የትናንትን የታሪክ ምዕራፍ ሲገልፅ ለዛሬ ያበቃውን ዕውነታ ይረዳል፡፡ ዛሬ የተገኘው ትናንት በተሠራው ጠንካራ ሥራ ነውና፡፡ ዛሬ ለተመዘገበው ውድቀትና ድክመት የትናንቱ አሻራ መኖሩ አይካድም፡፡ ትናንት ጥሩ ተሠርቶ ካለፈ ለዛሬው ብርታትን፣ ጥንካሬን፣ ዕድገትንና ወደ ፊት የመራመድ ውጤቶችን መለገሱ አይቀሬ ነው፡፡ ጉዞውና ውጤቱ የተገላቢጦሽ ሲሆንም ያንኑ መልክ ይላበሳል፡፡ የትናንት አባቶች የገነቡት ለዛሬዎቹ ልጆች ማረፊያና መኖርያ ሆኗል፡፡ አያቶች ለትናንቶቹ አባቶች እንዳወረሱት ሁሉ፡፡ የህይወት ዑደት ሳይቆም በመቀጠሉ ትናንት በተራው ለዛሬ አስረክቦ ‹‹ነበር›› ሆኖ ያልፋል፡፡ ዛሬም ለባለተረኛው ነገ አስረክቦ ይሰናበታል፡፡
በዚህ የጊዜ ዑደት ውስጥ ታዲያ ሁሉም የሚጠበቅበትን አበርክቶ ማለፍ ሰውኛ ግዴታው ነው፡፡ የትናንቶቹ ያስረከቡትን አስረክቦ ከማለፍ በተጨማሪ ሌላ ተደማሪ ሥራ መሥራት ይኖርበታል፡፡ መልካሙን አስፋፍቶ፤ የጎደለውን ሞልቶ፤ ህፀፅ ያለበትን አስተካክሎ፤ ችግሮችን አስወግዶ መጓዝ ከማንኛውም ዜጋ የሚጠበቅ መልካም ተግባር ነው፡፡ ሁሉም እንደሙያውና አቅሙ ከሠራ ቅብብሎሹ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ያልፋል፡፡ ህዝብና አገርን የሚጠቅሙ በርካታ ሥራዎች ዕውን እየሆኑ ይወጣሉ፡፡ ልማት ይስፋፋል፤ ድህነት ይቀጭጫል፡፡ ዕድገት ይፋጠናል፤ ኋላቀርነት ይዳከማል፡፡
የህይወት ጉዞ በጊዜ ዑደት ይቀጥላል፡፡ ዜጋ ያልፋል፣ ሌላ ይተካል፡፡ የያኔዎቹ የአድዋ ጀግኖች የህይወት መስዋዕትነትን በመክፈል አገራቸውን ሳያስደፍሩ ለትውልዱ በክብር አስረከቡ፡፡ የሚጠበቅባቸውን ሥራ ትናንት አከናውነው ለዛሬው ተረካቢ ትተው አለፉ፡፡ ከጥብቅ አደራ ጭምር፡፡ ባለተረኛው የዛሬው የበኩሉን ሠርቶ፤ ለለውጥ ተግቶ፣ የተጣመመውን አቅንቶ፣ ያረጀውን አድሶ፣ በተረከበው ላይ ጊዜና አቅሙ የፈቀደለትን ያህል ጨምሮ ለባለነገው እንዲያስረክብ በማሳሰብ ግዳጃቸውን ተወጥተው አልፈዋል፡፡
በየዓመቱ የካቲት 23 በመጣ ቁጥር የትናንቱ የአገር ወዳድነት ታሪክ በምልሰት ብቅ ይላል፡፡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ዓለም ትኩረትና ፊቱን ኢትዮጵያ ላይ እንዲያደርግ ካስገደዱት ጥቂት ክስተቶች መካከል አንዱና ዋናው ድል ነው-ዓድዋ፡፡
በ1888 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን ዓድዋ ላይ ድል በሆነው በጄኔራል ባራቴሪ በሚመራው የኢጣሊያ ወራሪ ሠራዊት ላይ ድልን ተቀዳጁ፡፡ ታሪክ አይሽሬ ዘመን ተሸጋሪ ደማቅ ታሪክን ፅፈው አለፉ፡፡ በዘመናቸው ዛሬም ድረስ ስማቸው ጎልቶ እንዲነሳ፤ ጀግንነታቸው ግዝፈት እንዲነሳ ያስቻላቸውን አኩሪ ተግባር ፈፀሙ፡፡ በትናንቱ ማንነታቸው ለዛሬው ትውልድ የሚጠቅም ተጨባጭና መልካም ተግባር አከናወኑ፡፡
የያኔዎቹ አባቶች ወራሪውን የጣልያን ጦር ለመመከት ደማቸውን አፈሰሱ፤ አጥንታቸውን ከሰከሱ፡፡ በዚህም ደማቅና አኩሪ ድልን ተላበሱ፡፡ በዓለም ዓቀፍ መድረክ ጎልቶ የሚታይ ታሪክን ፃፉ፡፡ የዛሬው ታድያ ጋሻና ጦር ሳያስፈልገው በታጠቀው ዕውቀትና ክህሎት በድህነት ላይ ድል ለመቀዳጀት ነው መዝመት የሚጠበቅበት፡፡ ዕውነታው ይህ ቢሆንም ታዲያ አያትና አባቶቹ ጣልያንን ለማባረር እንዳልተዋደቁ ሁሉ የዛሬው ትውልድ ጣልያን ለመግባት ደሙን በየበረሃው ማፍሰሱ ተገቢነት አይደለም፡፡
ተረካቢው ትውልድ ነገ፣ ከነገ ወዲያ…ወዲያ… በዛሬ ማንነቱ ስሙ ሊጠራና በታሪክ ሊዘከር ለህዝብና አገር ጠቃሚና ቋሚ ተግባር ማከናወን ግድ ይለዋል፡፡ የትናንቱ ከነበረበት ሳይጠፋና ሳይጎድል፣ ሠላማዊው አየር ሳይደፈርስ፣ መተሳሰብና አንድነቱ ይበልጥ ጎልብቶና ዳብሮ፣ አዛውንቶች ተከብረውና ተፈርተው፣ የተቸገሩ ተረድተው አኩሪ ታሪኩ በትውልድ ቅብብሎሽ ማለፍ ይኖርበታል፡፡ ስለሆነም ለነገ በሚጠቅመው ዛሬ ላይ ብዙ መሥራትና መትጋት ግድ ይላል፡፡ ዛሬ ለዛሬ እንጂ ለነገ ዋስትና አይሆንም፡፡ ለዛሬ የታቀደው በ24 ሰዓት ካልተከናወነ ነገ ሌላ ዛሬ ይጠብቀዋል፡፡ እናም ሁሉም በቀኑ ሊከወን ግድ ነው፡፡ የይደር ሥራ ትርፉ ነገ ላይ ጫና መፍጠር ነው፡፡ ስለሆነም የዛሬው በዛሬ ማለቅ አለበት፡፡
በአልደፈር ባይ ጀግኖች ልጆቿ ተከብራና ታፍራ የቆየችው አገር በስመ ገናናነትዋ እንድትቀጥል ዛሬን በደንብ መጠቀም ይገባል፡፡ ትናንት አኩሪ ገድል የፈፀሙ ጀግኖችዋ የሚዘከሩበትና የሚታወሱበት፣ አቅመ ደካሞች የሚጦሩበት፣ ህፃናት በነፃነት የሚቦሩቁበት፣ ወጣቶች ለዕውቀትና ክህሎት የሚሽቀዳደሙባት አገርን ለባለተረኛው ለማስረከብ ወሳኙ የዛሬ ሩጫ ነው፡፡ ይህን አለማድረግ ለነገ በማይጠቅም ዛሬ ላይ ከመኖር ያለፈ አይሆንም ድምር ውጤቱ፡፡
የጥቁር ኩሩ ህዝቦች ተምሳሌት የሆነችው አገር ተከብራና ታፍራ የምትጠራበት፣ በጀግኖች ልጆቿ በዓለም መድረክ ጎልታ የምትታይበት ታሪክ እንዲፃፍ ነው አደራው፡፡ በሰለጠነ የሰው ኃይልና በዘመነ መሣሪያ ሊወራት የመጣን ኃይል በውድ ልጆቿ መስዋዕትነት ከቅኝ ግዛት ወጥመድ ያመለጠችው አገር ዛሬም ስሟ ከፍ ብሎ እንዲሰማ፣ ሰንደቅ ዓለማዋ በክብር እንዲውለበለብ የትናንቶቹ ባለአደራዎች የሚጠበቅባቸውን አበርክተው ለዛሬው አስረክበው አልፈዋል፡፡ እናም የዛሬው አደራ ተረካቢ አደራውን መብላት የለበትም፡፡ ለመብላት ቢሞክር በቃር ከመሰቃየት አይድንም፡፡ በአደራ በሊታነቱም በታሪክ ሲወቀስ ይኖራል፡፡ ስለሆነም የተረከበውን አደራ ለነገው ባለተራ በክብር ማስረከብ ይኖርበታል፡፡ ለዛውም በተረከበው ላይ ብዙ ጨምሮና ጨማምሮ፤ ደምሮና ደማምሮ፣ አትርፎና አትረፍርፎ፡፡
በሠላማዊ አየር የተሞላችን አገር ሠላሟን ማደፍረስ ድርጊቱ አደራ ከመብላት አይተናነስም፡፡ ስለሆነም ዜጎቿ በነፃነት የሚንቀሳቀሱባትን አገር ሠላም አስጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ ግድ ይላል፡፡ ለህያው ፍጡራን ምቹ ሆና የተረከባትን ምድር መበከልና የተፈጥሮ ሚዛኗን እንድትስት ማድረግም ቅቡልነት የለውም፡፡ በህዝቦች መካከል ለዘመናት የዘለቀውን የአንድነትና የመተሳሰብን ካስማ ለማላላትና ለመንቀል መጣርም ለህዝብና ለአገር አለመጨነቅ ነው፡፡ ከሠላም የተጣላ ድርጊት መከወን በምንም መስፈርት ይቅርታን አያሰጥም፡፡
ብሔርና ጎሳ፣ ቀለምና ሃይማኖት እየለዩ ለመጠቃቀምና ለመጎዳዳት መነሳት ሳይሆን የአንድነት ጎዳናውን ማጠናከር ነው ጠቃሚው፡፡ መከፋፈል ከሂሳብ ስሌት ያለፈ ፋይዳ እንዳይኖረው መንቀሳቀስ ነው ጀብደኝነት፡፡ አገር ለምታና በልፅጋ ለዜጎቿ ምቹ እንድትሆን መሥራት ነው የአገር ተቆርቋሪነት፡፡ በግጭትና ሁከት ትርፍ እንደሌለ ተገንዝቦ ከዕኩይ ድርጊት መራቅና መታቀብ እንጂ የብጥብጥ ሃዲድን መቆናጠጥ ጉብዝና አይደለም፡፡
በሠላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ አካላትን የሚያውኩ ተግባራትን ማሳለጥ ከዕኩያን መድረክ እንጂ ከአርበኝነት ተርታ አያሰልፍም፡፡ በሕገ ወጥና ዕኩይ ድርጊት አርበኝነትን መናፈቅ ይከብዳል፡፡ የተሰጠውን ጊዜ ለመልካም ነገር ማዋል ነው አርበኝነት፡፡ የዛሬን ቀን ለነገ የሚበጅና የሚጠቅም ሥራ ሠርቶ ማለፍ ነው ጀግንነት፡፡ ዛሬን በዕኩይ ድርጊት ማሳለፍ ለነገ በማይበጅ ዛሬ ላይ መኖር ነው፡፡
ለሕዝብና ለአገር የሚጠቅም ነገን ለማየት ዛሬን በአግባቡ መጠቀምና ማልማት ያስፈልጋል፡፡ ልማትን የሚያደናቅፍ፣ ሠላምን የሚያደፈርስ፣ ሁከትን የሚነዛ፣ ግጭትን የሚያበረታታ ውጤቱ ከባድ ኪሳራ ነው፡፡ ዛሬውን በዚህ የማይደገፍ ሂደት ያሳለፈ የነገውን ጎዳና ያጨልማል፡፡ ስለሆነም ዛሬው ለነገ አይሆንም ማለት ነው፡፡ እናም ለነገ የማይሆነውን ዛሬ ከመኖር አለመኖሩ ይመረጣል፡፡
የትናንት አባቶችና እናቶች በጊዜያቸው የተገበሩትና የፈጸሙት አኩሪ ታሪክ ለዛሬው ትውልድ ከፍታ ሆነውለታል፡፡ ትናንታቸውን ለዛሬ ማደግና መለወጥ ተጠቅመውበታል፡፡ ስለሆነም ለነገ የሚሆነውን ዛሬ ሠርተውበታል፣ ተለውጠውበታል፣ ፍሬ አፍርተውበታል፣ ውጤት አስመዝግበውበታል፤ ደማቅ ታሪክ ከትበውበ ታል፡፡
የዛሬዎቹም ተረካቢዎች በዚህ የጀግንነት ታሪክ የመኩራታቸው ምስጢር የትናንቱ ብርታትና የልማት አርበኝነት ነው፡፡ እናም የዛሬው እንደ ቀደምቶቹ ለነገ የሚበጀውን ማቀድ፣ መተግበርና መፈፀም ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ሲሆን ታዲያ ለነገ የማይሆነውን ዛሬ ከመኖር ያለፈ አይሆንም ውጤቱ፡፡ ሁሉም በየዘመኑ የሚጠበቅበትን በአግባቡ መወጣት ይኖርበታል፡፡ ቀደምቶቹ ለእሱ ተጠቃሚነትና መለወጥ የተጉትን ያህል መድከም አለበት፤ ግዴታውም ነው፡፡
የጀግኖች ሰማዕታት አኩሪ ገድል የሚዘከርበት የዓድዋ ድል ቋሚ መታሰቢያ የሚሆን ሀውልትና ሙዚየም ለመገንባት እንቅስቃሴው ተጀምሯል፡፡ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በተለይ በታሪካዊው ገድላዊ ሥፍራ ዓድዋ ከተማ ከሶሎዳ ተራራ ግርጌ፡፡ ተራራውን የቱሪዝም መስህብ ለማድረግ የተጀመረው ጉዞ ዕውን እንዲሆን መትጋት ይገባል፤ ግዴታም ነው፡፡ ዓድዋን ለአብነት ጠቀስኩ እንጂ ለማንታችን ኩራትና ጌጥ የሆኑ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፤ እየተከናወኑም ይገኛል፡፡
የቀደሙቱ ትናንት ለዛሬው ዕድገትና ኩራት እንደደከሙት ሁሉ የዛሬው ለነገው መትጋትና መሥራት ግዴታው ነው፡፡ የተሻለች ነገን ለመፍጠር ርብርቦሹ መጠናከር አለበት፡፡ የዚህ መለኪያውና መስፈርያው ደግሞ ግልፅና አጭር ነው፡፡ ለሕዝብና ለአገር የሚጠቅም ሥራን ሠርቶ ማለፍ ብቻ፡፡ ሁሌም የልማትን፣ የሠላምን፣ የአንድነትን፣ የመከባበርን፣ የዕድገትን፣ የመቻቻልን፣ የመረዳዳትን፣ የመፋቀርን መልካም ጎዳና መከተል፡፡ ይህን ጎዳና አጠናክሮ መቀጠል፡፡

ሠላም ዘአማን

Published in አጀንዳ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።