Items filtered by date: Thursday, 08 March 2018

የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የንግድና የኢኮኖሚ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የንግድና ኢኮኖሚ ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር ስምምነት ላይ ደርስዋል።

የሁለቱ አገራት ሁለተኛው የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ ዛሬ በአዲስ አበባ ተኳሂዷል።

አገራቱ ግንኙነታቸውን በተለያዩ ዘርፎች የሚያጎለብት የፖለቲካ ምክክር ለማድረግ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነትም ተፈራርመዋል።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር ያላትን የንግድና ኢኮኖሚ ግንኙነት ለማሳደግ ቁርጠኛ ነች።

መንግስት በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች መሰማራት ለሚፈልጉ የአረብ ኤምሬቶች ባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋትን በማስፈንና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር በትብብር መስራት እንደምትፈልግም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ተለዋጭ አባል መሆኗ ለዚህ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ዶ/ር ወርቅነህ ተናግረዋል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ አል ናህያን በበኩላቸው የንግድና ኢኮኖሚ ግንኙነቱ እንዲጠናከር በአገራቸው በኩልም ፍላጎትና ዝግጁነት መኖሩን ተናግረዋል።

አገራቱ ግንኙነታቸውን በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በባህል ልውውጥ ማሳደግ የሚችሉባቸው ሰፊ እድሎች እንዳሉም ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት አስር ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ 98 ያክል የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች እየሰሩ ይገኛሉ። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያን የወጭ ምርቶች በማስገባት በመካከለኛው መስራቅ ሁለተኛዋ አገር ነች።

                                                                                                        

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር                                                                         

ቃል አቀባይ ጽ/ቤት

Published in የሀገር ውስጥ
Thursday, 08 March 2018 17:20

የብዙዎች መድን

ዝናቸውን ሰምተን መኖሪያቸውን ለማግኘት አልተቸገርንም፡፡ ከመካኒሳ አቦ አደባባይ ወደ ድልድዩ የሚወስደውን መንገድ ይዘን አለፍ እንዳልን ከመንገዱ በስተቀኝ የተሰበሰቡ ሰዎችን ተመለከትን፡፡ ሰዎቹ በእማማ ጆሮ ሻንቆ እጅ ታሽተው ለመዳን ወረፋ የሚጠብቁ ናቸው፡፡
ከቆርቆሮ አጥር ላይ ተለጥፋው እንደነገሩ በቆሙ አጠናዎች አናት ላይ ማዳበሪያ የተሸፈነች መጠለያ ትታያለች፡፡ በመጠለያዋ በተደረደሩት መኪናዎች ውስጥ እና በአጥሩ ጥግ ሰዎች ስማቸው እስኪጠራ ይጠባበቃሉ፡፡ ከደጅ ቤቱን ለመለየት ተቸገርን፤ መግቢያዋ ቀጭን ነበረች፡፡ ተጠግተን ‹‹እማማ ጆሮን ፈልገን ነበር›› የሚል ጥያቄ ስናቀርብ፤ ‹‹ዛሬ መጥታችሁ ዛሬውኑ መታከም አትችሉም፤ ለወረፋ መመዝገብም አቁመናል፡፡ እስከ ታኅሣሥ 2011 ዓ.ም ድረስ ሰዎች ተመዝግበዋል›› ተባልን፡፡ ለህክምና አለመምጣታችንን ብናስረዳም እማማ ጆሮ ጋር ለመቅረብ አልተፈቀደ ልንም፡፡
ለበር ጠባቂው ወጣት ጉዳዩን በዝርዝር ስናስረዳ ቀጭኑ አሸብር የእማማ ጆሮ ልጅ ካጀቡት ጎረምሶች ፈንጠር ብሎ ሊያነጋግረን ቀረበን፡፡ በትህትና ‹‹ምን ፈልጋችሁ ነው?›› የሚል ጥያቄ አቀረበ፡፡ እማማ ጆሮን ልናነጋግራቸው እንፈልጋለን፡፡ ከማለት ይልቅ ከየት እንደመጣን አስረዳን፡፡ ‹‹ አሁን ይህ ሁሉ ሰው ወረፋ እየጠበቀ ነው፡፡ ለቃለመጠይቅ አይመቻትም›› በሚል ምላሽ ሰጠን፡፡ ምን ይሻላል ስንባባል፤ ‹‹ዕሁድ ቀን ወይም ነገ የሕፃናት ተራ ስለሆነ፤ በምሳ ሰዓት መምጣት ትችላላችሁ›› ተባልን፡፡ ፈቃደኛ በመሆናቸው ተደስተን ተመለስን፡፡
በማግስቱ ሰባት ሰዓት አካባቢ እማማ ጆሮ ቤት ደርሰናል፡፡ ብዙዎች ልጆቻቸውን አቅፈው በር ላይ ተኮልኩለዋል፡፡ ግማሹ ሲወለድ ጀምሮ የታመመ፤ አንዳንዱ ቅጭት፤ ሌላው የልጁ እጅ የተጣመመበት፤ አንዳንዱ ደግሞ የልጁ እግር የተጥመለመለበት ብቻ ሁሉም የታመመ ልጁን ይዞ ስሙ እስኪጠራ ይጠብቃል የመዳንን ተስፋ ሰንቆ፡፡ ልጆቻቸውን አቅፈው የተኮለኮሉትን ሰዎች አልፈን በቀጭኗ በር ወደ ውስጥ ዘለቅን፡፡ ሳሎኑም እንዲሁ ልጆቻቸውን በታቀፉ ሰዎች ተሞልቷል፡፡ እማማ ጆሮ እንደገመትነው ምሳ እየበሉ አላገኘናቸውም፡፡
ከሳሎኑ አልፈን አጎንብሰን ወደ ቀጣዩ ክፍል ስንገባ አንዲት እናት ሕፃን ልጇን ታቅፋ ተቀምጣለች፡፡ ሴትየዋን እና የተኮለኮለውን ዕቃ አልፈን ወደ ውስጥ ስንዘልቅ የእማማ ጆሮ ማከሚያ እና ሌሊት ደግሞ የሚተኙባት ክፍል ደረስን፡፡ ክፍሉ አልጋቸውን እና አንድ ሳጥን ይዟል፡፡ እጅግ ጠባብ ነው፡፡ የእማማ ጆሮ ቤት የተሠራው እንደአሮጌዎቹ የአዲስ አበባ ቤቶች ሁሉ ከጭቃ ሲሆን፤ አልጋው እማማ ጆሮን፤ ለመታሸት የመጣውን የአራት ዓመት ልጅ እና የልጁን እናት ይዟል፡፡ እማማ ጆሮ የልጁን እግር እያሹ ነው፤ ልጁም እንባውን እያፈሰሰ፡፡ እናቱ ተጠግታ የምትባለውን እየሰማች ልጇን በኀዘን ስሜት ትመለከታለች፤ መቼም ልጇ እንዲድንላት ትፈልጋለችና እንባው ቢፈስም ከማዘን በስተቀር ከእማማ ጆሮ እጅ ልትፈለቅቀው አልሞከረችም፡፡
እማማ ጆሮ ‹‹የቀኝ እግሩ ሎሚ አፈንግጧል፤ በንፁሕ ማር እና በሎሚ እሠሪው ብዬሽ ነበር፡፡ አልሰማሽኝም፤ ለምን አላሰርሽውም?›› የሚል ጥያቄ ለልጁ እናት አቀረቡ፡፡ እናትም ‹‹የግራውን ያሉኝ መስሎኝ ያሰርኩት ግራ እግሩን ነው›› ስትል፤ ‹‹ ልጅሽ ተረከዙ መርገጥ ጀምሯል፤ እስከ አሁን ቀኙን በትክክል አስረሽለት ቢሆን ኖሮ እግሮቹ አይለያዩም ነበር፡፡ በደንብ ይራመድ ነበር፡፡ እስኪ የግራ እጁ ጣቶች ተዘረጉ?›› ብለው በዳበሳ እጁን አገኙት፡፡ ‹‹በእርግጥም የተጨበጡት ጣቶቹ ተዘርግተዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም በጣቶቹ አንጓዎች ላይ ስጋው እንደሚስማር ጭንቅላት አብጧል›› ብለው ማሸታቸውን ሲቀጥሉ ልጁም አንጀት የሚያንሰፈስፍ ለቅሶውን ቀጠለ፡፡ ይህችኛዋ ጨርሳ ስትወጣ ሌላኛዋ ልጇን አቅፋ ገባች፡፡
ዕድሜው ሁለት ዓመት አይሞላም፡፡ እናት ልብሱን አወላልቃ ሰጠቻቸው፡፡ ገና መላ ሰውነቱን ሲነካኩት ልጁ ጩኸቱን አቀለጠው፡፡ የቀኝ እጁን ሙሉ ለሙሉ ጨብጦታል፤ መዘርጋት የሚችል አይመስልም፡፡ ልጁ በጣም እያለቀሰ በመረበሹ እናቱ‹‹አጥቢው፤ አባብይው›› ተባለችና እኛ ሥራችንን ጀመርን፡፡
እማማ ጆሮ ለብዙዎች መድህን የሆነውን የማሸት ሥራ ከጀመሩ አስራ ሦስት ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡ እናት እና አባታቸው አዋላጅ እና ወጌሻ ነበሩ፡፡ ሆኖም እርሳቸው ዓይነ ስውር ስለነበሩ የወላጆቻቸውን ዕውቀት መውረስ አልቻሉም፡፡ ነገር ግን የልጃቸው ዓይነስውር መሆን ያሳስባቸው የነበሩት የእማማ ጆሮ ወላጆች ለልጃቸው ‹‹ከኛ የተሻለ ጥበብ ይስጥሽ!›› ብለው መርቀዋቸው ነበር፡፡ እማማ ጆሮም የሚያምኑት አሁን ብዙዎችን ለማከም የቻሉት በወላጆቻቸው ምርቃት እና በፈጣሪያቸው ፈቃድ ነው፡፡
በአንድ ተቋም ውስጥ በዣንጥላ ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበረ ሲሆን፤ ድርጅቱ ከሰረ ተብሎ ሲበተኑ እርሳቸው ቤት ተቀመጡ፡፡ ወድቀው የተሰበሩ እና ወለም ያላቸው አዋቂዎች እንዲሁም የተቀጩ ሕፃናት ወደ እርሳቸው እየመጡ ሲታሹ ስለዳኑ ወሬው ከሰፈር አልፎ ሲዛመት የታካሚው ቁጥር ጨመረ፡፡ ሰዎች በወረፋ መታከም ሲጀምሩ ጎረቤቶች ቅር አላቸው፡፡ በትንሿ ግቢ ውስጥ ተጠጋግተው የሚኖሩት ሰዎች የእማማ ጆሮ በረንዳ በሰው መጨናነቁ አስከፋቸው፡፡ ዝናቸው ሲነገር ሰው ከትንሿ ግቢ አልፎ አካባቢውን ማጥለቅለቅ ያዘ፡፡ የእማማ ጆሮ ታካሚዎች እና አስታማሚዎች ሽንት ቤት ሲፈልጉ ወደ ግቢው የጋራ ሽንት ቤት መላካቸው የጎረቤት ቅሬታ እና ክስ በዛ፡፡ እማማ ጆሮ ሽንት ቤቱን ቢያስጠርጉም፤ ጎረቤቶቻቸው አልረኩም፡፡ እማማ ጆሮ ይህን ሲነግሩን እንባ እየተናነቃቸው ነበር፡፡
ሰው በወጌሻም ሆነ በዘመናዊ ህክምና ካርድ ከማውጣት ጀምሮ ክፍያ እያስከፈለ ከኪራይ ቤት ፎቅ እስከ መገንባት እየደረሰ ነው፡፡ እርሶ ለ13 ዓመታት ብዙዎችን አክመዋል፡፡ እንዴት ገንዘብ እጅዎት ላይ የለም በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ ‹‹ህልሜ ገንዘብ መሰብሰብ ሳይሆን ሰዎችን ማዳን ነው፡፡ ለአዋቂ ሰው በጣም የተጎዳም ቢሆን ለስድስት ወራት ቢታከምም የመጨረሻ የክፍያ ጣራ ሁለት ሺ ብር ብቻ ነው፡፡ ይህ ላለው ሰው ነው፡፡ የሌለው ደግሞ አምስት ሳንቲም ሳይከፍል ይታከማል፡፡ የለኝም ያለ በ500 ብር ለብዙ ጊዜ የሚታከምም አይጠፋም፡፡ ለሕፃናት እና ለልጆች ደግሞ የማስከፍለው የመጨረሻ ትልቁ ክፍያ አንድ ሺ ብር ብቻ ነው፡፡ ይህ የመጨረሻ ከፍተኛው ዋጋ ነው፡፡ በዚህ ገንዘብ አራት ልጆቼንና ራሴን አስተዳድራለሁ፡፡ ከዚህ አልፎ መሬት መግዛትና ቤት መሥራት አልችልም›› ይላሉ፡፡
እማማ ጆሮ እንደሚገልጹት፤ ሰዎችን ሲያሹ አንዳንዶቹ ያስመልሳቸዋል፡፡ በተዝናና ቦታ ምቹ መፀዳጃ ቤት ባለመኖሩ እጅግ የታመሙ ሰዎችን ለማሸት ተቸግረዋል፡፡ ምቹ መፀዳጃ ቤት ለማሠራት ካለባቸው የገንዘብ እጥረት ባሻገር እጅግ የተቸገሩት በቦታ እጦት ሳቢያ ነው፡፡ የመኪና አደጋ የደረሰባቸው፣ የአጥንት ስብራት ያጋጠማቸው ሰዎች ከጎንደር፣ ከደሴ፣ ከወልቂጤ ከሌሎችም ከተሞች እና ክልሎች የሚመጡትን የሚያስተንግዱት በዛችው በጠባቧ ቤታቸው ነው፡፡ በቀን የማስተናግደው 25 ሰው ነው። ከዚያ በላይ የሆኑት ተመዝግበው ለሌላ ጊዜ ይቀጠሩ፤ አትቀበሉ ቢሉም፤ ከዚያ በላይ በስቃይ ያሉና አስቸኳይ ዕርዳታ የሚፈልጉ ያጋጥማሉ፤ በዕቅፍ እና በዊልቸር በአምቡላንስ የሚመጡ አሉ፡፡ እነዚያን ለሌላ ቀን መቅጠር አስቸጋሪ በመሆኑ እነርሱን ይቀበላሉ፡፡
‹‹ስብራት፣ ውልቃት፣ ጨጓራ እና ሌሎች ህክምናዎችን መስጠት ብችልም የምፈልገውን ያህል መሥራት አልቻልኩም›› ይላሉ፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት ጀምሮ ጥያቄ ቢያቀርቡም፤ ቅያሬ ቤትም ሆነ ቦታ ማግኘት አልቻሉም፡፡ የዳኑ ሰዎች መቀመጫ አልጋ እየገዙ ይሰጧቸዋል፡፡ ታካሚዎቹ እርስ በራሳቸውም ይረዳዳሉ፡፡ ነገር ግን የቦታ አለመኖር ትልቅ ፈተና ሆኖባቸዋል፡፡ ‹‹ያም ሆኖ አይከፋኝም፤ ዓይኖቼ ሰዎቼ ናቸው›› የሚሉት እማማ ጆሮ ለ13 ዓመት ሲሠሩ ምንም ዓይነት ችግር እንዳላጋጠማቸው ይናገራሉ፡፡
ከመከፋት ውጪ ስለደስታዎትንም ይንገሩን? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ በእዝል የመጡ ሰዎች ቆመው ሲሄዱ ሲያዩ እጅግ የሚደሰቱ መሆኑን ነገሩን፡፡ ታዋቂ ሰዎችን ጨምሮ የተለያዩ ለዓመታት መራመድ ያቃታቸው ሰዎች እየዳኑ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ከሁሉም በላይ ሁለቱም ትከሻቸው የወለቀባቸውን አንድን ሰው በአንድ ቀን ትከሻቸውን ቦታው ላይ መመለሳቸው እጅግ እንዳስደሰታቸው ያስታውሳሉ፡፡ ከአሜሪካ፣ ከእሥራኤል፣ ከዑጋንዳ እና ከደቡብ አፍሪካ ዝናቸውን የሰሙ መጥተው መዳን ችለዋል፡፡ ይህ ለእርሳቸው ትልቅ ደስታና ኩራት ነው፡፡
እማማ ጆሮ 63ኛ ዓመታቸውን ይዘዋል፡፡ ዕድሜ አይታወቅም ብለው ልጆቻቸውን ለመተካት እያስተማሩ ነው፡፡ ነገር ግን ከአንድ ከወንድማቸው ልጅ ውጪ የእርሳቸው አንድ ወንድ ልጅም ሆነ ሌሎች የሚያሳድጓቸው ልጆች እንደርሳቸው ያለድካም ማሸት አልቻሉም፡፡ ሆኖም ግን ልጆቹ ለእያንዳንዱ ህመም ምን ዓይነት አስተሻሸት እንደሚያስፈልግ ማወቅ ችለዋል፡፡
ወይዘሮ መሰረት ግዛው በእማማ ጆሮ እጅ ታሽተው ከዳኑ ሰዎች ውስጥ አንዷ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደነገሩን፤ ወድቀው እግራቸው አልሄድ ሲላቸው ቤተሰቦቻቸው ታዝለው በመምጣት በአንድ ቀን ለውጥ አግኝተው ከእማማ ጆሮ በተሰጣቸው ምርኩዝ መራመድ ችለዋል፡፡ በታሹ በአራተኛው ቀንም ሙሉ ለሙሉ ድነው ሥራ መጀመራቸውን ገልጸውልናል፡፡
ልጃቸውን ሲያሳሹ ያገኘናቸው እናት ብርቄ አጥሌም፤ ሲወልዱ ልጃቸው ላይ በደረሰ ጉዳት መራመድ አለመቻሉን ከሦስት ዓመት በኋላ እማማ ጆሮ ጋር ሲያመጡት ለውጥ ማየታቸውን እና ልጃቸው እያነከሰ መራመድ መጀመሩን ነግረውናል፡፡
እኝህን ሴት የዚህ ቀን እንግዳ ያደረግናቸው ሴቶች የብዙዎችን ህይወት ለማቃናት በየዘርፉ የሚሠሩትን ሥራና ውጤታማነታቸውን ለማሳየት ነው፡፡ እኛም ለእማማ ጆሮ ረጅም ዘመን ተመኘን።

ምህረት ሞገስ

 

 

Published in ማህበራዊ
Thursday, 08 March 2018 17:16

የቤት ለእምቦሳ ቱሩፋቱ

ያለፉት 18 ዓመታት ለወይዘሮ እመቤት ስንሻው ቀላል የሚባሉ አልነበሩም፡፡ በእነዚህ ዓመታት በግለሰብ ቤት ተከራይተው ብዙ ስቃይን አይተዋል፡፡ ዛሬ መለስ ብለው እያስታወሱት ‹‹ በአከራዮች የደረሰብኝ በደል ተቆጥሮ አያልቅም» ይላሉ፡፡ በእርግዝናም ሆነ በወሊድ ወቅት፤ ውሃ አፈሰሳችሁ፣ ብዙ ቆጠረ፣ እንግዶች በዙ የሚሉ ወቀሳዎች ይበዙባቸው ነበር፡፡ ይባስ ብሎም ምክንያታዊ ያልሆነ ድንገተኛ የኪራይ ጭማሪ ተከትሎ ቤት እስከማስለቀቅ የደረሰ በደል አሳልፈዋል፡፡
«ከሁሉም በላይ ያዘንኩበትና የማልረሳው አጋጣሚ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ሳልዘጋጅ 'ቤቱን ስለምንፈልገው ልቀቂ!' ተብዬ በአውዳመት ልጆቼን ያንከራተትኩበትን ጊዜ ነው» ይላሉ፡፡ ይሄም ፈጣሪያቸውን እስከማማረር አድርሷቸዋል፡፡ ይሁንና ከሁለት ዓመት በፊት በተላለፈው የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ ዕድለኛ ሆነው ከተከራይነት ወደ ቤት ባለቤትነት ተሸጋግረዋል፡፡ እናም እርሳቸውም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው ከጫና መገላገላቸውን ይገልጻሉ፡፡
ወይዘሮ እመቤት የደረሳቸው ባለ ሁለት መኝታ ክፍል ቤት ስምንት ሺ ብር እንደሚከራይ ቢሰሙም ከኪራይ የሚገኘው ገቢ ሳያጓጓቸው በራሳቸው ቤት መኖር ከጀመሩ ከራርመዋል፡፡ ምክንያቱም በተከራይነት ያዩትን መከራ ደግመው ማየትን አይሹም፡፡ «ልዩነቱ የሰማይና የምድር ያህል ነው›› በማለት ልዩነቱን የሚገልጹት ወይዘሮዋ፤ በተለይም ነፃነትን በማጎናፀፍ በኩል የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ ነው፡፡
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት መንግሥት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ቁርጠኛ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ በተለይም በ1987 ዓ.ም በጸደቀው የኢፌዴሪ ህገ-መንግሥት፤ ሴቶች በአገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ እኩል ተሳትፎ እንዲኖራቸው፤ ተቋማዊና መዋቅራዊ አሠራሮችን ለመዘርጋት በር የከፈተ ነው፡፡ ሴቶች በአገሪቱ ማናቸውም ጉዳዮች ላይ ያላቸውን እኩል ተሳታፊነትም አረጋግጧል፡፡ በተለይም አንቀጽ 25 ጾታን መሰረት ያደረገ ማግለል በህግ ፊት ተቀባይነት እንደማይኖረው ‹‹ሁሉም ሰዎች በህግ ፊት እኩል ናቸው በመካከላቸውም ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በህግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል...» በማለት ያስቀምጣል፡፡ በተጨማሪም ‹‹የሴቶችን እኩል ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚደነግገው አንቀጽ 35 ደግሞ የሥራ ቅጥርና የመሬት ባለቤትነትን ጨምሮ በሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል መብት እንዳላቸው በሰፊው ያትታል፡፡
ይሄን ድንጋጌ በተግባር ከሚተረጉሙ ማሳያዎች መካከል ደግሞ ልክ እንደ ወይዘሮ እመቤት ሁሉ በርካታ ሴቶችን የቤት ባለቤትነት ማንሳት ይቻላል፡፡ መንግሥት ለሴቶች ልዩ ተጠቃሚነት በማመቻቸት የቤት ባለቤት ማድረጉ ከሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር በሴቷ ላይ ይደርስ የነበረው ማህበራዊ ቀውስን በመቀነስ ረገድ የማይናቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግና ያለባቸውን የኑሮ ጫና ለማቃለል በመንግሥት እየተሠሩ ካሉ ሥራዎች መካከል የጋራ መኖሪያ ቤቶች በልዩ ኮታ ማለት በዕጣ ከሚተላለፈው ከ70 በመቶ ድርሻ በተጨማሪ 30 በመቶውን የሚሆነው ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተድረጓል፡፡ ከዚህ አኳያ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ለህዝብ ከተላለፉት 237 ሺ ቤቶች ውስጥ 54 በመቶ በአዲስ አበባ፤ በክልሎች ደግሞ 37 በመቶ ሴቶች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
በተለይም በአዲስ አበባ በ11 ዙሮች ከተላለፈው 175 ሺ ቤቶች ውስጥ 52 ሺ500 ቤት የሚሆነው ለሴቶች ነው የደረሰው፡፡ በተመሰሳይ በ2009 በጀት ዓመት ለተጠቃሚዎች በተለላፈው በ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት መርሐ ግብር ከ972 ቤቶች ውስጥ 425 የሚሆነው ለሴቶች መድረሱን መረጃው ያመለክታል፡፡
በተመሳሳይ መንግሥት በአገሪቱ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዲያድግ በርካታ ሥራዎችን በመሥራቱ በየዘርፉ የሴቶች ውሳኔ ሰጪነት ከፍተኛ እድገት አሳይቷል። በ1987 ዓ.ም ሁለት በመቶ ብቻ የነበረው የሴት ፓርላማ አባላት ቁጥር በ2007 ዓ.ም ምርጫ ማግስት ቁጥራቸውን ከ38 በመቶ በላይ አሳድጎታል። ይሄ መሻሻል በክልል ምክር ቤቶችም በስፋት ተስተውሏል፡፡
ሕብረተሰቡ በሴቶች ላይ አሁንም ድረስ ሙሉ ለሙሉ ያልተወገደውን ኋላቀር አስተሳሰብ ለመቅረፍ የአስተምህሮና አመለካከትን የመቀየር እንዲሁም ሴቶች የራሳቸው የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲኖራቸው ከማድረግ አኳያ ረጅም ርቀት መጓዝ ተችሏል። ሴቶች በአገሪቱ በሚካሄዱ የተለያዩ የልማት፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና የመልካም አስተዳደር እንቅስቃሴዎችም ግንባር ቀደም ተሳታፊና እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግም አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
ወይዘሮ ዘውድነሽ ብርሃኑ «መንግሥት ለሴቶች በሠራው ሥራ አንዷ ተጠቃሚ እኔ ነኝ» በማለት የበርካታ ሴቶችን ምስክርነት ይጋራሉ፡፡ እርሳቸውም የሁለት ልጆች እናት ሲሆኑ ባለቤታቸውን በሞት በመነጠቃቸው ምንም ዓይነት የገቢ ምንጭ አልነበራቸውም፡፡ በመሆኑም ልጆቻቸውን ይዘው ከሰው ቤት ተጠግተው ነው የኖሩት፡፡ በየሰው ቤት እየተዘዋወሩ በልብስ ማጠብና አሻሮ በመቁላት በሚያገኙት ሽርፍራፊ ሳንቲም የዕለት ጉርሳቸውን ከመሸፈን ባለፈ ልጆቻቸውን ለማስተማር እንኳን አልቻሉም ነበር፡፡
ችግራቸውን የተረዱ በጎ አድራጊ ሰዎችና ዘመዶች ድጋፍ ያደርጉላቸው እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ ባስጠጓቸው ግለሰቦች አነሳሽነት እንደቀልድ የተመዘገቡት የኮንዶሚኒየም ቤት መርሐግብር ዓመታትን ቆጥሮ በአስረኛው ዙር ባለዕድል አድርጓቸዋል፡፡ «አሁንም ድረስ እውነት እውነት አይመስለኝም» ይላሉ፡፡ ምክንያታቸውም፤ እንደእርሳቸው ያለ ምስኪን ሰው እስከ ህይወቱ መጨረሻም ቢሆን የቤት ባለቤት ይሆናል የሚል ግምት አልነበራቸውም፡፡
«በአንዳንድ ዘመዶች ድጋፍና በማገኛት 10 እና 20 ብር እየቆጠብኩና እቁብ በመጣል ቅድመ ክፍያዬን ለመክፈል ችያለሁ» የሚሉት ወይዘሮ ዘውድነሽ፤ በአሁኑ ወቅት በዕጣ የደረሳቸውን ቤት በማከራየት ቋሚ የገቢ ምንጭ ማግኘት ችለዋል፡፡ ይህም ልጆቻቸውን ለማስተማርና የተሻለ ቤት ተከራይተው ለመኖር እየደጎማቸው መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
ሴቶችን የቤት ባለንብረት ለማድረግ ተግባራዊ ተደርጎ እየተሠራበት ካሉ መርሐግብሮች አንዱ በህብረት ሥራ ማህበራት አካኝነት መሬት ሰጥቶ ራሳቸው ቤት እንዲገነቡ ማድረግ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በአሁኑ ወቅት በሁሉም ክልሎች ከ17 ሺ በላይ ማህበራት ተደራጅተው 331 ሺ ለሚሆኑ ሴቶች መሬት በማቅረብ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
በየካ አባዶ ኮንዶሚኒየም ቤት ተጠቃሚ የሆኑት ወይዘሮ ብዙወርቅ ዳንኤል፤ መንግሥት የሴቶችን ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሠራ ያለውን ሥራ ያደንቃሉ፡፡ ሴት የንብረትና የሀብት ተካፋይ እንዳትሆን እንደባህል ስር የሰደደ የአመለካከት ችግር ባለባት አገር ውስጥ በጥቂት ዓመታት ብቻ በርካቶችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ የሚያበረታታ ነው፡፡
ከ26 ዓመታት በላይ በኪራይ ቤት መኖራቸውን የሚያነሱት ወይዘሮ ብዙነሽ፤ የኮንዶሚኒየም ቤት ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤን በማስለመድ ረገድ የማይናቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ «በግለሰቦች ቤት ውሃና መብራት እንደልብ መጠቀም ስለማንችል የምናበስለው በከሰል አልያም ደግሞ በጋዝ ምድጃ ነበር፡፡ ይህም ጊዜና ጉልበትን የሚወስድ በመሆኑ በተለይም ለሴቶች ከፍተኛ ጫና ይፈጥርብናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ሁሉንም ሥራ በኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች በመሆኑ ድካምና ጊዜያችንን ቀንሶልናል፤ ወጪውንም በመታደግ ረገድ የተሻለ ነው» ይላሉ፡፡
በተጨማሪም ከፍሳሽ አወጋገድ ጋር ተያይዞ በግለሰብ ቤቶች በሚኖሩበት ጊዜ ከጎረቤት ጋር ግጭት ውስጥ ይገቡ ነበር፡፡ «እኛ የቱንም ያህል አካባቢያችንን ብናፀዳ ሌላው ግን ቆሻሻውን ደጃፉ ላይ የሚደፋ በመሆኑ ሁልጊዜ አለመግባባቶች ይፈጠሩ ነበር፤ ፍሳሽንም ማስወገጃ ስፍራ ባለመኖሩም እንደጉንፋንና መሰል በሽታዎች በተደጋጋሚ ይይዙን ነበር» ይላሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን በሚኖሩበት የካ አባዶ አካባቢ አዲስ መንደር እንደመሆኑ ፅዱ፥ ከከተማ ግርግርና ጫጫታ የራቀ መሆኑ ጤናማና ሰላማዊ ኑሮ ለመኖር ዕድል ፈጥሮላቸዋል፡፡
ወይዘሮ ብዙነሽ የኮንዶሚኒየም ቤት ከደረሳቸው ወዲህ በግለሰብ ቤት ይኖሩ ከነበረው በተሻለ የማህበራዊ ህይወት መሳተፍ መቻላቸውን ይገልጻሉ፡፡ ከበርካታ ሰዎች ጋር እንዴት በፍቅር መኖር እንደሚቻል ተምረውበታል፡፡ «ከዚህ ቀደም አከራዮችን መፍራት ከሰላምታ ባሻገር ከየትኛው ጎረቤት ጋር የጠበቀ ግንኙነት መፍጠር አልሻም ነበር፡፡ አሁን ግን ያለምንም ጫና ከጎረቤቶቼ ጋር በሁሉም ማህበራዊ ህይወት እየተሳተፍኩ ነው» ይላሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ከጎረቤቶቻቸው ጋር እድርና ማህበር አቋቁመዋል፡፡ በየሳምንቱ እየተገናኙ ስለአካባቢያቸውና ስለአገር ጉዳይ ያወጋሉ፤ ይመካከራሉ፤ የተቸገረም ካለ ይደጋገፋሉ፡፡ ይህም የመንግሥት ልዩ ጥረት ውጤት እንደሆነ ያምናሉ፡፡
«የቤት ተጠቃሚ በመሆኔ ከፈጠሪ በታች መንግሥትን አመሰግናለው» የሚሉት ወይዘሮ ብዙነሽ፤ በቀጣይም በመንግሥት ሊሠራ ይገባል የሚሉትንም ሃሳብ ይጠቁማሉ፡፡ «መንግሥት ቤት ለሌላቸው ታሳቢ አድርጎ ይህንን መርሐ ግብር ቢያዘጋጅም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሰዎች የመኖሪያ ቤት እያላቸው የደረሳቸው ናቸው፡፡ ስለሆነም መንግሥት ቤት የሌላቸውን አጣርቶ በትክክል መስጠት ይኖርበታል›› ይላሉ፡፡ በሌላ በኩልም ከሚበሉት ቆጥበው ዕጣቸውን ለዓመታት እየጠበቁ ያሉ በርካታ ሴቶችንም የኑሮ ጫና ለመቀነስ የተጀመሩ ቤቶችን ግንባታ በማጠናቀቅ ማስተላለፍ እንደሚገባውም ነው ያስገነዘቡት፡፡
የሴቶችን በዓል በየዓመቱ ከማክበር ባለፈ መንግሥት በህገመንግሥቱ በተደገገው መሰረት የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ ተጨማሪ ሥራዎችን መሥራት ይገባል፡፡ መላው ህብረተሰብም የመንግሥትን ጥረት በመደገፍ ከሴቶች ጎን መቆም ይገባዋል፡፡

በማህሌት አብዱል 

የስኬት አንደበት

ከስኬታማዎቹ መንደር ወደ ጋሞ ጎፋ ዞን አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ጫኖ ዶርጋ ቀበሌ ልውሰዳችሁ፡፡ በዚህ ቀበሌ ውስጥ «ለምለም የጫኖ ዶርጋ ሴቶች ካሳቫ ማቀነባበሪያ መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማህበር›› ይገኛል፡፡ ማህበሩ ሲቋቋም ዓላማ አድርጎ የተነሳው በአካባቢው የሚለማውን የካሳቫ ተክል እሴት በመጨመር ለአባላት የተሻለ ገበያ በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ ነው፡፡
ማህበሩ የዛሬ አምስት ዓመት ሲመሰረት ዓላማውን ደግፈው ከቤታቸው የወጡት ሴቶች ሃያ ብቻ ነበሩ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ማህበሩን በአመራርነት በማገልገል ላይ የሚገኙት ወይዘሮ ንግሥት ማሞ አንዷ ናቸው፡፡ ስድስት ልጆች ወልደው ሲያሳድጉ ከቤት ወጥተው አያወቁም፡፡ ሰፊ ቤተሰብ ይዘው በዓመት በሚሰበስቡት የግብርና ውጤት ኑሯቸውን መምራት ለእርሳቸው ከባድ ነበር፡፡ የለምለም የጫኖ ዶርጋ ሴቶች ካሳቫ ማቀነባበሪያ መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማህበር አባል ከሆኑ ወዲህ ግን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው ጨምሯል፡፡
ስድስት ልጆቻቸውን ያስተምራሉ፡፡ የቤት አያያዛቸውን፣ አመጋገባቸውን፣ ንፅሕና አጠባበቃቸውን በመቀየር ዘመናዊ ኑሮ ለመኖር ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ የባለቤታቸውንም እጅ አይጠብቁም፡፡ ከማሳቸው ከሚሰበስቡት ካሳቫ ተክል ሽያጭና ከማህበራቸው የትርፍ ክፍፍል የሚያገኙትን ገንዘብ ለሚፈልጉት አገልግሎት ለማዋል በመቻላቸውም በራስ ገቢ መተዳደርንና ማዘዝን ተለማመደዋል፡፡ በአካባቢውም በማህበር ተደራጅቶ ሥራ መፍጠር የተለመደ ባለመሆኑ እንደርሳቸው በኑሮ ችግር ውስጥ የሚገኙ ብዙ ሴቶችም የኢኮኖሚ አቅማቸውን እየገነቡ ይገኛሉ፡፡
የአካባቢያቸውን ሴቶች በማደራጀት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ያደረጋቸውን የጃፓን ዓለምአቀፍ ተራድኦ ድርጅት (ጃይካ)ን ያመሰግናሉ፡፡ እርሳቸው እንዳሉት ጃይካ ስለ ማህበር አደረጃጀት ግንዛቤ በመፍጠር፣ የካሳቫ ተክልን በማቀነባበር ዙሪያ ስልጠና ሰጥቶና አደራጅቶ ወደሥራ እንዲገቡ አስፈላጊውን ድጋፍ አድርጎላቸዋል፡፡ ወይዘሮ ንግሥት የአመራርነት ሚናም መወጣት የቻሉት በማህበር በመደራጀታቸው እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡ አስተዳደርን እየተለማመዱ፣ የእወቀት አድማሳቸውን እያሰፉ፣ የኢኮኖሚ አቅማቸውንም እየገነቡ በለውጥ ውስጥ መሆናቸው አስደስቷቸዋል፡፡
ገቢ ሊያሳድግ በሚችል ነገር ላይ ለመሰማራት መንገድ ባለመኖሩ ለዓመታት በችግር ላይ የቆዩትን ሴቶች ወደኋላ ሲያሰቡ ይቆጫሉ፡፡ «አሁንም አረፈደም» የሚሉት ወይዘሮ ንግሥት በአሁኑ ጊዜ የካሳቫ ተክል በኩንታል ሽያጩ እስከ ስምንት መቶ ብር ደርሷል፡፡ ቀደም ሲል ሦስት መቶና ከዚያ በታች ነበር፡፡ የአካባቢው ሴቶች ጠንክረው ካመረቱና የማህበሩ አባልም ሆነው ከተንቀሳቀሱ ውጤታማ እንደሚሆኑም መክረዋል፡፡
በአካባቢያቸው ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ማህበር ሊቋቋም መሆኑን በሰሙ ጊዜ ግንባር ቀደም አባል መሆናቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ አበበች ዓለሙም እንዳጫወቱን የሚተዳደሩት በግብርና ሥራ ነው፡፡ በዓመት ከሚደረሰው የግብርና ውጤት በስተቀር ሌላ ገቢ አልነበራቸውም፡፡ በዓመት የሚያገኙት የግብርና ምርት ለቀለብ ውሎ፣ ከላዩ ላይ ተሸጦ ፍላጎት አያሟላም፡፡ ኑሮን ለመለወጥ ደግሞ አይታሰብም፡፡
ከማሳቸው የሰበሰቡትን ካሳቫ ለማህበራቸው በመሸጥ፣ ከማህበራቸውም የትርፍ ክፍፍል በማግኘታቸው በኑሯቸው ላይ ለውጥ ማምጣት ጀምረዋል፡፡ ቤተሰባቸው ጥቂት መሆኑ ደግሞ ኑሯቸው ላይ ፈጣን ለውጥ ለማምጣት አልተቸገሩም፡፡ ከማጀት መውጣታቸው የተለያዩ አማራጮችን ለማየት ዕድል አግኝተዋል፡፡ ለመለወጥ ያላቸው አስተሳሰብም ከፍ ብሏል፡፡ ይሄ ሁሉ የመጣው በማህበር በመደራጀታቸው እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ማህበራቸው አቅሙን እያሳደገ ሲሄድ ደግሞ እርሳቸውም ገቢያቸው እንደሚያድግና የበለጠ እንደሚለወጡም ተስፋ አድርገዋል፡፡
የማህበሩ መቋቋም የተለያዩ ጥቅሞችን አስገኝቷል፡፡ የካሳቫ ተክል ቶሎ የሚበላሽ በመሆኑ ተቀቅሎ ለምግብነት የሚውለው በጣም ጥቂቱ ብቻ ነበር፡፡ በአብዛኛው የሚውለው ለከብት መኖ ነው፡፡ መቀነባበሩ በተፈለገ ጊዜ ለመመገብ አስችሏል፡፡ ገቢ እየተገኘበት በመሆኑም ካሳቫን በወቅቱ ሰብስቦ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግም በአካባቢው ተለምዷል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ለማህበሩ በማቅረብ ገቢ እያገኙ ነው፡፡ አባላት ምርታቸውን ለማህበሩ በመሸጥ፣ በአባልነታቸው ደግሞ ማህበሩ አቀነባበሮ ከሚሸጠው ትርፍ በማግኘት ተጠቃሚነታቸው የላቀ ሆኗል፡፡
እንዲህ ስለውጤታቸው ያጫወቱን ለምለም የጫኖ ዶርጋ ሴቶች ካሳቫ ማቀነባበሪያ መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማህበር አባላት ተቀቅሎ ለምግብነት የሚውለውን የካሳቫ ተክል አቀነባብሮ በዱቄት መልክ በማዘጋጀት ለገበያ በማቅረብ ገቢ ማግኘት እንደሚቻል ስልጠና ሲሰጣቸው «እስኪ እንየው» በሚል ስሜት ነበር ስልጠናውን የወሰዱት፡፡ ቀቅለው የሚመገቡት ካዛቫ ዱቄት ይሆናል ብለውም አልገመቱም፡፡ ስልጠናውን ወስደው በተግባር ያዩት አባላቱ ካሳቫ ብቻውንም ሆነ ከሌላ የእህል ዘር ጋር አደባልቆ በማዘጋጀት ገንፎ፣ ቂጣ፣ ዳቦ እንጀራ እያደረጉ መመገብ እንደሚቻል በተግባር አረጋግጠዋል፡፡ በገበያ ላይ ተፈላጊ ሆኖ ገንዘብ እያስገኘላቸው ነው፡፡
የለምለም የጫኖ ዶርጋ ሴቶች ካሳቫ ማቀነባበሪያ መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሮ ንግሥት እንደነገሩን፤ ማህበሩ የማቀነባበሪያ ፋብሪካ ከመክፈት ጎን ለጎንም ማህበሩን ሊያሳድግ በሚችል የተለያዩ የገቢ ማስገኛ መስኮች ላይ ለመሰማራት አቅዷል፡፡ የማህበር አባላት ቁጥርን ለመጨመርም ግንዛቤ በመፍጠር የተጠናከረ ሥራ ለመሥራት ተዘጋጅቷል፡፡ ማህበሩ እንዲያድግና የሴቶችም ተጠቃሚነት እንዲጎለብት የደቡብ ክልል አስተዳደር የሥራ ቦታ በመስጠትና በተለያዩ ድጋፎች ከጎናቸው እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡ ማህበሩ በአሁኑ ጊዜ 20ሺ 543 ብር የሚገመት ተንቀሳቃሽ ንብረት፣ ቋሚ ደግሞ 89ሺ 687ብር አፍርቷል፡፡
ማለዳ ከእንቅልፏ ተነስታ በእርሻና በማጀት ውስጥ በሥራ ስትማስን የምትውለው የገጠሯ ሴት ለራሷም ሆነ ለቤተሰቧ የኑሮ ለውጥ ሊያመጣላት የሚችል በአደባባይ ስለመኖሩ ለማወቅ ዕድሉ የላትም፡፡ ነግቶ ሲመሽ በተመሳሳይ ሥራና የኑሮ ጫና ውስጥ የምትገኘው የገጠሯ ሴት አጋጣሚውን አግኝታ በጫና ውስጥ አልፋ ለስኬት ስትበቃ ማየት ያስደስታል፡፡ አርአያነቷም ሌሎችን ያነቃቃል፡፡
እንዲህ በስኬት የለውጥ ጎዳና ላይ ለመድረስ በአገሪቷ አምስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሴቶች በህብረት ሥራ ማህበር ተደራጅተው በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ከፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከወንዶች ጋር የተደራጁ ቢሆኑም አብዛኞቹ አባላት ሴቶች ናቸው፡፡ የአቅም ግንባታ አግኝተው በመደራጀት ውጤታማ ሊያደርጋቸው በሚችል የሥራ መስክ ላይ እንዲሰማሩ ኤጀንሲው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ እንደ ጃይካ ካሉ ተቋማት ጋር በጋራ እየሠራ ይገኛል፡፡
በኤጀንሲው የሥርዓተ ፆታ ክፍል አስተባባሪ ወይዘሮ ሐመልማል ክብሬ እንደነገሩን፤ የሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በህብረት ሥራ አዋጅ ፖሊሲና ስትራተጅ ውስጥ ተካቶ እየተሠራ ሲሆን፣ ሴቶችን በተለየ ሁኔታ ተጠቃሚ የሚያደርግ አዲስ መመሪያና ደንብ ተዘጋጅቷል፡፡ አዋጁ ቀደም ሲል የነበረ ቢሆንም፣ የሴቶች የአመራርነት ሚና እንዲጎለብት አስገዳጅ የሆነ መመሪያና ደንብ ስላልነበረው አዲስ ማውጣት አስፈልጓል፡፡
መመሪያና ደንቡ ሴቶች በማህበር ውስጥ በየደረጃው ባለው የሥራ መዋቅር ላይ የአመራርነት ሚናቸው ከፍ እንዲል ያስገድዳል፡፡ ብቻቸውን ተደራጅተው የበለጠ ለመጠናከር ለሚፈልጉም ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል፡፡ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመን የማህበር አባላትን ከ30 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 50 በመቶ ማድረስ፣ ሴት የማህበር አመራሮችን ደግሞ 30 በመቶ ለማድረስ ግብ ተይዞ እየተሠራ ነው፡፡
ወይዘሮ ሐመልማል እንዳሉት፤ ሴቶች በማህበር እንዲደራጁ ብቻ ሳይሆን፤ የቁጠባ ባህል አዳበረው የተሻለ የሥራ ዕድል በመፍጠር የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲገነቡ ይበረታታሉ፡፡ በብድርና ቁጠባ ተጠቅመው በተለያየ የሥራ ዘርፍ የተሰማሩትን ምርጥ ተሞክሮ ያላቸውን መድረክ በመፍጠር፣ምርትና አገልግሎ ቶቻቸውን በኤግዚቢሽንና ባዛር እንዲያቀርቡ ሁኔታዎችን በማመቻቸትና የማበረታቻ ሽልማት በመስጠት ጠንክረው እንዲሠሩ ይበረታታሉ፡፡ ተሞክሮን የማስፋት ሥራም ጎን ለጎን ይከናወናል፡፡ ምርጥ ተሞክሮ ያላቸው ሴቶችን የማበረታታቱ ተግባር አምና በደቡብ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በሐረሪ ተከናውኗል፡፡ በየዓመቱ ሰኔ ወር ላይ በሚከበረው በዓለም አቀፍ የህብረት ሥራ ማህበር ቀን ላይ በሚከናወነው የእውቅና ሥነሥርዓት ላይ በብድርና ቁጠባ ገንዘብ ተጠቅመው በተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ የተሰማሩና ከፍተኛ ሀብት ያፈሩ ሴቶችን ማግኘት መቻሉን ነግረውናል፡፡
የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማጎልበት በአገር ደረጃ የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማሳደግ በማህበር፣ በጥቃቅንና አነስተኛ በተለያዩ አደረጃጀቶች በህብረት ሆነው ሠርተው እንዲለወጡ፣በስልጠና በማብቃት፣የገንዘብ ብድርና ቁጠባ በማመቻቸት የተከናወኑት ተግባራት ይጠቀሳሉ፡፡
በፖለቲካው ዘርፍም በአገሪቷ በአምስት ዙሮች በተካሄዱ ምርጫዎች በመጀመሪያው የምርጫ ዘመን ምክርቤት የገቡት ሴቶች ቁጥር ወደ 13 አካባቢ ነበር፡፡ በአምስተኛው ዙር የምርጫ ዘመን ደግሞ ቁጥራቸው 212 ደርሷል፡፡ በቁጥር ከመነጋገር ባለፈ የህዝብ ውክልና ይዘው ወደ ምክርቤቱ የገቡ ሴቶች በምክርቤቱ በሚተላለፉ ውሳኔዎች ውስጥ ተጽኖ ፈጣሪ ሆነው ሚናቸውን በመወጣትና በአጠቃላይ ስለተሳትፏቸው መነጋገር ላይ ደርሰዋል፡፡
በህይወት ፍልስፍናቸው፣ በታታሪነታቸው፣ በመንፈሰ ጠንካራነታቸው፣ በንግግር አዋቂነታቸው፣ በሥራ ትጋታቸው፣ በአመራር ብቃታቸው፣ በአዛኝነታቸውና በለጋስነታቸው የሚታወቁና በስብዕናቸውም የሚያስቀኑ ሴቶች ቢኖሩም የሚገኙት በመብራት ተፈልገው ነው፡፡ ከህብረተሰቡ ግማሽ ያህል የሆኑት ሴቶች አብዛኞቹ በማህበራዊና በፖለቲካ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ አነስተኛ ነው፡፡የኢኮኖሚ ጥያቄያቸው ያልተፈታላቸውም ጥቂት አይደሉም፡፡

በለምለም መንግሥቱ 

Published in ፖለቲካ

ከአባቷ አቶ መዝገቡ መክብብና ከእናቷ ከወይዘሮ አየለች መኩሪያ አብራክ ይችን ምድር የተቀላቀለችው መስከረም 27 ቀን 1939 ዓ.ም ነው፡፡ የትውልድ ቦታዋ ደግሞ በአሁኑ ስያሜው አዳማ በያኔው ናዝሬት ከተማ ምንጃር ጎዳና ነው - አንጋፋዋ ደራሲ ሽቶ መዝገቡ ገና ታዳጊ እያለች ወላጆቿ በመለያየታቸው ከእናቷ ጋር ወደ አዲስ አበባ መምጣት ግድ የሆነባት ደራሲ ሽቶ፤ ቤተሰቦቿ ቢለያዩም ከአባቷ ጋር የነበራት የጠበቀ ግንኙነት አልተቋረጠም ነበር፡፡ አባቷ ከሌላ ከወለዷቸው ልጆች ጋርም መልካም የሆነ መግባባት ነበራት። ከእንጀራ እናቷ ጋርም ቢሆን በህይወት እስከ ነበሩበት ድረስ የእናት ያህል መቀራራብ ነበራቸው፡፡
ደራሲ ሽቶ ልክ እንደብዙዎቹ ኢትዮጵያ ውያን ሕፃናት ፊደል የቆጠረችው ቄስ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ቀጥላም በመኖሪያዋ አካባቢ በሚገኘው የቀድሞው ልዑል መኮንን፤ ቀጥሎም ስሙ ተለውጦ ወሰንሰገድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ 2ኛ ክፍል ተምራለች፡፡
በዚህ መካከል እናቷና እርሷ ይኖሩበት የነበረውን ሰፈር በመልቀቃቸው ትምህርት ቤቱንም መቀየር ግድ ሆነባት፡፡ የድሮው ደጃዝማች በየነ መርዕድ ትምህርት ቤት እንደገና ከአንደኛ ክፍል ጀምራ መማር ጀመረች፡፡ በዚሁ ትምህርት ቤት እስከ 1956 ዓ.ም ድረስ የተማረች ሲሆን፣ 8ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈታናንም በ1956 ወስዳለች፡፡
በ1957 ዓ.ም ወደ 9ኛ ክፍል በጥሩ ውጤት በማለፏ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገባች፡፡ በትምህርት ቤት ቆይታዋ የቅርቤ የምትላትና ከግማሽ ምዕተዓመት በላይ ጓደኛዋ የሆነቸውን ወይዘሮ ሙላቷ ሀረገወርቅን አትረሳትም፡፡ ወይዘሮ ሙላቷ ሚዜዋ ስትሆን እስከአሁን ድረስም በጓደኛነት ለ53 ዓመታት አብረው ዘልቀዋል፤ አሁንም አብሮነታቸው አላቋረጠም፡፡
ደራሲዋ የ9ኛ ክፍል ተማሪ ሳለች ነበር የመጀመሪያ ድርሰቷ የሆነውን ‹‹ሰው በመሆኔ ደከምኩ›› የተሰኘውን የተውኔት መፅሐፍ ያሳተመችው፡፡ ይህን የተውኔት መፅሐፍ የፃፈችው ቀን ቀን በመማር፤ ሌሊት ሌሊት ደግሞ ለድርሰቱ ጊዜ በመስጠት እንደነበር የምትናገረው ደራሲ ሽቶ፤ በወቅቱ ሌሊት ተጽፎ የተጠናቀቀውን ድርሰት ለአማርኛ መምህሯ እንዲያርሙ ትሰጣቸዋለች፡፡ መምህሯም ጽሑፉን አርመው የሠራቸው ሥራ ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ነግረው ሲመልሱላት፤ የሥዕል መምህሯ ደግሞ በድርሰቷ ውስጥ የተካተቱትን ሥዕሎች በመሥራት አጋርነታቸውን በመግለጽ አበረታተዋታል፡፡
ደራሲ ሽቶ በትምህርት ቤት ቆይታዋ «በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ» እንዲሉ ትምህርቷን በአግባቡ እየተማረች ጎን ለጎን ደግሞ ድርስቷን በአንድ ላይ ታስኬደዋለች፡፡ ትምህርት ቤት ሳለች ትልቁን ጊዜ የምትሰጠው ለክርክር ነበር፡፡ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት ከመሰሎቿ ጋር መከራከርን ታዘወትራለች፡፡
ደራሲ ሽቶ በትምህርት ቤት ቆይታዋ ትመኝ የነበረው ነርስ ለመሆን ነበር፡፡ ይህ ፍላጎት የእርሷ ብቻ ሳይሆን የአባቷም ጭምር ነበር፡፡ ይሁንና ይህን ምኞቷን የሚያስለውጥ አንዳች ከስተት ተፈጠረ፡፡ የ10ኛ ክፍል ተማሪ በነበረችበት ወቅት ነርስ መሆን የሚፈልጉ የሚማሩበትን ቦታ እንዲመርጡ ሲደረግ ስለነርሶች ለማውቅ የሚሠሩበትን ቦታ ማየት ነበረባት። ሄዳ ያየችው ጉዳይ ግን የጠበቀችው አልነበረም። ነርሶቹ ቁስለኞችና ሌሎች ታማሚዎች ሲያክሙ በማስተዋሏ ሙያው ለእርሷ እንደማይሆን አመነች፤ ነርስ የመሆን ሐሳቧንም ቀየረች፡፡ ሌላው ሐሳቧን የመቀየሯ ምክንያት ደግሞ ወደ ነርስ ትምህርት ቤት ሄዳ ስታይ «ነርስ መሆን ከተፈለገ ሻይም ሆነ ቡና መጠጣት አይቻልም» የሚለው መመሪያ የሻይ ሱሷን መተው ለማትችለው ለእርሷ ከባድ እንደሆነባት ታስታውሳለች፡፡
በትምህርት ቤት ቆይታዋ አንድ የማይረሳት ነገር ቢኖር የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪዎች ካናዳውያን ነበሩና በቅጥር ጊቢው ውስጥ ተማሪዎቹ ቁጠባን እንዲለምዱ ታስቦ ባንክ መኖሩን ነበር፡፡ ተማሪዎች በአንድ ብርም ይሁን በሃምሳ ሳንቲም የባንክ አካውንት እንዲከፍቱ ይደረግ ነበር፡፡ ከቤት ወደ ትምህርት ቤት ከትምህርት ቤት ደግሞ ወደ ቤት የምትመላለ ስበት የአውቶቡስ ትኬት እንድትቆርጥ የሚሰጣትን ብር ግማሽ መንገዱን ከጓደኛዋ ጋር በእግሯ ስለሚሄዱ ግማሹን ባንክ ታስቀምጠው እንደነበር አልዘነጋችውም፡፡
የድርሰቶቿ ይዘት
ደራሲ ሽቶ የሴት ደራሲያን ቁጥር ጥቂት በነበረበት ከዛሬ ግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት በ1957 የመጀመሪያ ሥራዋን፣ በ1959 ደግሞ ሁለተኛው ድርሰቷን ለንባብ አብቅታለች፡፡ የመጀመሪያው ‹‹ሰው በመሆኔ ደከመኩ›› ሲሆን፤ ሁለተኛው ርዕስ ደግሞ ‹‹በመወለዴ እንዲህ መሆኔ›› ይሰኛል።
የመጀመሪያው ድርሰቷ የሚያጠነጥነው በሁለት ወጣቶች ዙሪያ ሲሆን፣ ሁለቱ ወጣቶች የሚፋቀሩና የሚተሳሰቡ ናቸው፡፡ ይሁንና በሌላ ወጣት ጣልቃ ገብነት በመካከላቸው መተማመን እንዳይኖር ይደረጋል፡፡ ነገር ግን የፍቅረኛሞቹ የዓላማ ጽናታቸው ከፍ ያለ በመሆኑ እና የሰው ወሬ ባለመስማታቸው አበቃለት የተባለው ፍቅራቸው ዳግም ህይወት ዘርቶ በመጋባትና ልጆችን በማፍራት ሰላማዊ ህይወት መግፋታቸ ውን የሚዳስስ ነው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ የትዳርን ሕይወት የሚያስቃኝ ሲሆን፤ የጥንዶች መለያየት የሚያስከትለውን መከራና ጭንቀት ይዳስሳል፡፡ ውሃ አጣጭ የተባለ አባወራ፤ አሊያም እማወራ በማንኛውም አይነት ሁኔታ ከአጋሩ ሲለይ አሊያም ከአጋሯ ስትለይ የሚያሳድረውን ጭንቀት ነው ለማሳየት የሞከረችው፡፡
ደራሲዋ፣ በዚህ በሁለተኛ ድርሰቷ ላይ የተመለከተው ሃሳብ ‹‹የእኔንም ህይወት የሚነካ ነው›› ስትል ትናገራለች፡፡ ምክንያቷ ደግሞ እርሷም በልጅነቷ ወላጆቿ ተለያይተው በማደጓ ‹‹የገፈቱ ቀማሽ ነኝ›› ስትል አጫውተኛለች፡፡ ጽሑፉ በሴት ልጅ ላይ የሚደርስን ፈተና የሚያስቃኝ ነው፡፡
‹ሰው በመሆኔ ደከምኩ›› የተሰኘውን ድርሰቷን ከኦቴሎ ቴአትር ጋር ታነፃፅረዋልች፡፡ የእያጎ ገጸ ባህሪ በመጽሐፏ ውስጥ ተካቶ መገለጹን ትናገራለች፡፡ በዚሁ ድርሰቷ ውስጥ በዚያን ጊዜ የሠርግ ወጪ እንዲቀነስ የሚያበረታታ ሐሳብ ተካቶበታል፡፡ ድርሰቷ «ያለፈውንና የአሁኑን ትውልድ ማያያዝ የሚችል ታሪካዊ ነው ቢባል የሚበዛበት አይደለም» ትላለች፡፡ በዚህ ድርሰት ላይ ጥናታዊ ጽሑፎችም ተሠርተውበታል፡፡
ጽሑፍ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ፣ ስነ ጽሑፍና ፎክሎር ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ‹‹በኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍ ጉዞ ቀደምት ሴት ደራሲዎች አጭር ቅኝት›› በሚል ንዑስ ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ፤ በ1950ዎቹ አስርት ስለተነሱና ቀዳሚ ብለው የለዩአቸውን ሴት ደራሲያንን ጠቅሰዋል፡፡ እነዚህም አራት ሲሆኑ፣ ከእነርሱም መካከል አንዷ ደራሲ ሽቶ መዝገቡ ናት በማለት ጠቅሰዋል።
የተከፈለ መስዋዕትነት
ቀን ቀን ትምህርት፤ ሌሊት ሌሊት ደግሞ ድርሰቱን በመጻፍ ስትታትር የነበረችው ደራሲ ሽቶ፤ በእናቷ ፍጹም ደጋፊነት ጽሑፉ እልባት በማግኘቱ ለህትመት ዝግጁ ቢሆንም ማሳተሚያው ከወዴት ይምጣ?
እናትም ልጃቸው ገና በአፍላ ዕድሜዋ እንደሌሎቹ አቻዎቿ መቦረቅና መፈንደቅ ሳያምራት አንገቷን ደፍታ ውድቅት ላይ ስትጽፍ የቆየችው ጽሑፍ ተጠናቆ በማየታቸው ቢደሰቱም፤ የህትመቱ ጉዳይ ግን እጅግ አሳስቧቸው እንደነበር ደራሲዋ አጫውታኛለች፡፡
ደራሲ ሽቶ ሌሊት ሌሊት ቁጭ ብላ በምትጽ ፍበት ጊዜ እናት ካጠገቧ አይለዩም፡፡ ልጃቸው የዕለት ጽሑፏን አጠናቃ ወደመኝታዋ ስትሄድ እርሳቸውም ወደ መኝታቸው ይሄዳሉ፡፡ ማለዳ ደግሞ ከእርሷ ቀድመው ነቅተው ይቀሰቅሷታል፡፡ እያንዳንዷን እቅስቃሴዋን በመከታተል አቅማቸው የፈቀደውን ያህል አግዘዋታል፡፡
ደራሲ ሽቶ እንቅልፏንና የልጅነት ጊዜዋን መስዋዕት ያደረገችለት ድርሰቷ ተጠናቆ ባየች ጊዜ ያማጠችለት ሥራዋ ታትሞ ማየት ናፈቀች፤ ወደ ማተሚያ ቤትም ብቅ ብላ ስለገንዘቡ ጠየቀች፡፡ ነገር ግን የማሳተም ምኞትና ፍላጎት እንጂ ለህትመት እንዲበቃ የሚያስችል ቤሳ ቢስቲን አልነበራትም፡፡ እንዲያም ሆኖ እጇን አጣጥፋ መቀመጥ አልፈለገችም፡፡ የእናቷንም የገንዘብ አቅም ጠንቅቃ ታውቅ ስለነበር በወለድ ከሚያበድሩ ሰዎች እንዲበደሩላት ትጠይቃቸዋ ለች፡፡ እናትም ሳያቅማሙ ወደ ስፍራው በማቅናት በወለድ ሊበደሩ ይጠይቃሉ ‹‹መጽሐፍ ለማሳተም ከሆነማ ግድየለም ያለወለድ ይውሰዱ›› ተብለው በወቅቱ ለህትመት ያስፈለጋትን ሁለት ሺ ብር ይዘው ከች አሉላት፡፡ ድርሰቱም ታተመላት፡፡
ሁለት ሺ ብሩ ወለድ አይኑረው እንጂ ሊመለስ ግድ መሆኑን የሚያውቁ እናቷ፤ የተወሰደባቸውን የአባታቸውን ቦታ አስመልሰው ሽጠው ሊከፍሉላት ቢያስቡም፤ አይገባዎትም ይባላሉ፡፡ ጉዳዩንም ለሰዎች ሲያማክሩ ‹‹ጃንሆይ ወደ ደብረዘይት ሲሄዱ ነጠላሽን አንጥፈሽ ለምኝ›› የሚል ምክር ያገኛሉ። እንደተባሉት ያደርጋሉ፡፡ ይሁን እንጅ ምክሩ አዎንታዊ ምላሽ አላገኘም ነበር፡፡ ጄነራል አሰፋ ደምሴ በተባሉ የእልፍኝ አስከልካይ በኩል ቢቀርቡም እንዳሰቡት አልተሳካም፡፡
ድርሰቱ ከታተመ በኋላ እናት ከመጽሐፉ አንዱን አንስተው ለጄነራሉ ‹‹ልጄ የጻፈችው መጽሐፍ ነው›› ብለው ይሰጧቸዋል፡፡ እርሳቸ ውም ያነቡና ‹‹መጽሐፉን በወርቅማ ጽሑፍ ሸፋኑን አስጽፋ ታምጣና ለጃንሆይ እስጣቸ ዋለሁ›› ባሉት መሰረት መጽሐፉ ጃንሆይ እጅ ይገባል፡፡
ንጉሡም ‹‹ይህንን መጽሐፍ ያሳተመችውን ልጅ አቅርብልኝ›› ይላሉ። ግራና ቀኝ የአገሪቱ ሚኒስትሮች በቆሙበት ደራሲ ሽቱ ቀረበች፤ እጅ ነስታም በቆመችበት ወቅት፤ ጃንሆይ ‹‹ይገርማል! ከርዕሱ የድርሰቱ፤ ከድርሰቱ የርዕሱ›› በማለት ለሚኒስትሮች ይናገሩና ወደ እርሷ መለስ ብለው ጥቂት ጥያቄዎችን ይሰነዝሩላታል፡፡ ገንዘቡን ከየት አምጥታ እንዳሳተመችው ይጠይቋታል፡፡
የዚያኔዋ ኮረዳ ሽቶም ፈጠን ብላ እናቷ በወለድ ተበድራ መሆኑን ትገልጽላቸዋለች፡፡ ወዲያው ለህትመት የወጣው ብር እንዲሰጣት ካዘዙ በኋላ ‹‹ምን አደርግልሽ ዘንድ ትወጀያለሽ›› ሲሉ ይጠይቋታል፡፡ እርሷም ቀልጠፍ ብላ ‹‹ውጭ አገር ሄጄ የጋዜጠኝነት ትምህርት መማር እፈልጋለሁ›› ስትል ትመልስላቸዋለች፡፡
በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር በነበሩት ምናሴ ኃይሌ በኩል ጉዳዩ እንዲያልቅላት ትዕዛዝ ይሰጣሉ፡፡ እርሳቸውን ቀርባ ባነጋገረቻቸው ወቅት ‹‹ገና የ9ኛ ክፍል ተማሪ በመሆንሽ 12ኛ ክፍልን መጨረስ ይኖርብሻል›› ትባላላች። ይሁን እንጅ በወቅቱ ያንን ማድረግ ባለመቻሏ ደግማም ሳትሄድ በዚያው መቅረቷን አጫውታኛለች፡፡
ከ46 ዓመት በኋላ ድጋሚ ህትመት
በ1957 ዓ.ም ያሳተመችውን የመጀመሪያ መጽሐፏን በድጋሜ በ2003 ዓ.ም እንዲሁም ለሦስተኛ ጊዜ በ2006 ዓ.ም በስፖንሰር አማካይነት ለህትመት አብቅታለች፡፡ ሁለተኛውን ማለትም በ1959 ዓ.ም የታተመውን ድርሰቷን ግን ስፖንሰር ባለማግኘቷ እስከአሁን ለማሳተም አልቻለችም፡፡
ደራሲዋ በሁለት ዓመት ውስጥ ሁለት የድርሰት ሥራዎችን ገና በአፍላ የወጣትነት ዕድሜዋ ለንባብ ማብቃቷ ‹‹አጀብ›› የሚያሰብል ነበር፡፡ በወቅቱ በውስጧ ይንተገተግ የነበረው የስነ ጽሑፍ ፍቅር ዛሬም ከ53 ዓመት በኋላም አልበረደም፡፡
አሁን በሦስተኛ መጽሐፏ ብቅ ልትል የፈለገችበት ጉዳይ ትኩረቱን ያደረገው የእናቶች ሙያ ላይ ሲሆን፤ በተለይም ኢትዮጵያውያን የሚዋቡበት የባህል ልብስ መነሻ እናቶች ስለመሆናቸው የሚዳስስ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም እርማት ላይ ስትሆን ጽሑፉ የሚካተተው በኢ ልቦለድ ውስጥ መሆኑን አጫውታኛለች፡፡ መፅሐፉን ከጀመረች አምስት ዓመት ሆኗታል። በነርቭ ህመም ምክንያት ኮምፒዩተር እንደልብ መጠቀም ባለመቻሏ ብታዘገየውም አሁን ግን እየተሻላት ስለሆነ በቅርቡ አጠናቃ ለንባብ እንደምታበቃው ተናግራለች፡፡ ይህንን ሥራዋን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአማርናኛ ቋንቋ፣ ስነ ጽሑፍና ፎክሎር ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋውን በማማከር ላይ እናዳለች ገለጻልኛለች፡፡
ያለጥፋት እስራት
ደራሲ ሽቶ በማህበራዊ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ተሳትፎዎችን አድርጋለች፡፡ ሰውን ያስቀይማል ብላ የምታስበው ነገር ከለ ላለማድረግ በብዙ ትደክማለች፡፡ በተቻላት ሁሉ ከሰዎች ጋር በሰላምና በፍቅር መኖርን ትመርጣለች፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ውስን ሰዎች ክፋትን እንዳደረጉባት ታስታውሳለች።
ደራሲዋ በአንድ ወቅት አንዳች በማታውቀው ጉዳይ ተጠርጥራ ለስድስት ዓመታት ያህል ወህኒ ቆይታ ተለቃለች፡፡ ከእስር ከተፈታች በኋላ ግን ማህበራዊ ጉዳይ መሳተፍን ‹‹ዕርም ይሁንብኝ›› ስትል ነው ያጫወተችኝ፡፡ ቀበሌ አካባቢም ሆነ ሌሎች ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ትሳተፍ ነበር፡፡ ኢህአዴግ እንደገባ አካባቢ በደርግ አባልነቷ(ኢሰፓ) ምክንያት ለሦስት ወራት ያህል መታሰሯን ትገልጻለች፡፡ በ1988 ዓ.ም ደግሞ ለምስክርነት ትፈለጊያሽ ተብላ በሄደችበት ጊዜ ለአንድ ወር ታስራለች፡፡
በማታውቀውና ባላደረገችው ለስድስት ዓመት ከስምንት ወር ያለምንም ጥፋት መታሰሯ ቢያንገበግባትም ያጠፋችው ነገር ባለመኖሩ የህሊና ክስ የለባትም፡፡ ነገር ግን አንደ እግር እሳት ሆኖ ሁሌም የሚፈጃት ነገር ቢኖር፤ ሁለ ነገሯን አሳልፋ ትሰጣት የነበረቸውን ወላጅ እናቷን በእስር ላይ ሳለች ህይወቷ በማለፉ ሳትቀብራት መቅረቷ ነው፡፡
ቤተሰብ
ከመጀመሪያ ባለቤቷ ጋር የተዋወቀችው በአጎቷ የልጅ ልጅ ሠርግ ላይ ሲሆን፤ ከተዋወቁ በኋላ ሠርጋቸውንም ያደረጉት በ1959 ዓ.ም ሚያዝያ ወር ላይ ነበር፡፡ ከተጋቡ በኋላ በመካከላቸው በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት በ1971 ዓ.ም ቢለያዩም ሦስት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ሁለተኛ ባለቤቷን በ1975 ዓ.ም አግብታ ከእርሱም አንድ ልጅ አፍርታለች፡፡ በጠቅላላ የሦስት ሴትና የአንድ ወንድ ልጅ እናት ስትሆን፣ አሁን ቅድመ አያት ሆናለች፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ኑሮዋን ያደረገችው ከልጅ፣ ልጅ፣ ልጇ ጋር ነው፤ በኑሮዋም ደስተኛ እንደሆነች ነግራኛለች፡፡
የሥራ ሁኔታ
ደራሲ ሽቶ ትምህርቷን 10ኛ ክፍል ላይ አቁማ በኮካ ኮላ ፋብሪካ በፀሐፊነት ተቀጠረች፡፡ በሥራ ላይ እያለች ያቋረጠችውን ትምህርቷን ተግባረ ዕድ በማታው መርሐ ግብር በመማር 12ኛ ክፍልን አጠናቀቀች፡፡ በኮሜርስ ትምህርት ቤት ደግሞ የፀሐፊነት ኮርስ ወስዳለች፡፡ ኮካ ኮላ ፋብሪካ እየሠራችም የሠራተኞችንና የአሠሪዎችን ስምምነት በተመለከተ በማህበሩ ጸሐፊ ሆና አገልግላለች፡፡ ሥራዋን ለቃ ከወጣችም በኋላ ማህበሩን ሳትለቅ ለብዙ ዓመታት ሠርታለች፡፡
በሌሎች መስሪያ ቤቶችም በኮንትራትና በቋሚነት አገልግላለች፡፡ የከተማ ልማት መስሪያ ቤት በፀሐፊ ሆና ሠርታለች፡፡ በ1988 ዓ.ም በጡረታ እስከ ተገለልች ደረስ በህዝብ ግንኙነት ሙያ አገልግላለች፡፡
ቅሬታ
በ1976 ዓ.ም አካባቢ የደራሲያን ማህበር ባደረገላት ጥሪ መሰረት ወደ ተጋበዘችበት ስፍራ አቀናች፤ የመጡት ደራሲያን ሁሉ ታሪካቸውን እንዲናገሩ ጥያቄ ስለቀረበላቸው ተናገሩ፡፡ እርሷም ከተናጋሪዎቹ አንዷ ነበረችና ከተናገረች በኋላ በእርሷ ታሪከ ተደንቀው ስለነበር በሶቬየት ህብረት የትምህርት ዕድል እንዲሰጣት ተወሰነ፡፡ ይሁንና ዕድሉን ለሌላ ሰው አሳልፈው እንደሰጡባት ታስታውሳለች፡፡ በዚህም ውስጧ ስላዘነ ‹‹እናንተንም መታወቂያችሁንም አልፈልግም›› ብላ ከማህበሩና ከጽሑፉ ዓለም ለመለየት ወሰነች፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን በውስጧ ያለው የስነ ጽሑፍ ፍላጎት መንተግተጉን አላቆመም ነበር፡፡
ማንም ሰው ቢሆን የራሱ የሆነ መልካም ነገር ይኖረዋል፡፡ እንደየ አቅሙም ለአገሩም ሆነ ለአካባቢው አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት ታምናለች፡፡ በአንድ ወቅት ደግሞ ደራሲ ሽቶ፣ አንድ መርሐ ግብር ላይ በመጠራቷ ተገኝታለች። ልቧን የሰበረው ይህ መርሐ ግብር ደራሲያን የታደሙበት ሲሆን፤ ለስርዓቱ ማድመቂያ የተዘጋጀውን ኬክ እንደ አንጋፋ ደራሲነቷ መቁረስ የነበረባት እርሷ ሆና ሳለች ሌላዋ እንስት ደራሲ ‹‹አንጋፋ›› ተብላ እንድትቆርስ በመደረጉ ቅር ተሰኝታለች፡፡ አንጋፋነቷን ታሪክ ጎልጉሎ አንድ ቀን እንደሚያወጣው ትናገራለች፡፡
የሴት ደራሲያኑ እጅግ አነስተኛ ቁጥር ይዘው ባለበት ወቅት ሁለት አስተማሪና ገንቢ የሆኑ ድርሰቶችን በመፃፏ ያገኘችው ሽልማት እንዳለ ብዬ ጠየቅኳት፡፡ ‹‹እኔ ከጃንሆይ ካገኘሁት ማበረታቻ በስተቀር ሌላ አላየሁም›› በማለት ቅሬታ በተቀላቀለበት ስሜት መለሰችልኝ፡፡
መልዕክት
ደራሲ ሽቶ ከምንም ነገር በላይ ማንበብ ትወዳለች፡፡ የአማርኛ መምህራን አንብቡ የሚሏቸውን መጽሐፍት በደስታ ቀድማ በማንበብ ትታወቃለች፡፡ ሰው ቤት እንኳ በእንግድነት ሄዳ ምግብ ከሚያቀርቡላት የሚነበብ መጽሐፍ ቢሰጧት ትመርጣለች፡፡ ባጋጣሚ እንኳ ያየችው መጽሐፍ ካለ እንዲያውሷት ለምና ታነባለች፡፡ ከዚህም የተነሳ የቃላት አጠቃቀም አይደለም የፊደላትን አጣጣልና በየትኛው ቃል ውስጥ የትኛው ፊደል እንደሚገባም ጠንቅቃ ታውቃለች፡፡ እንዲያውም አሁን አሁን የምታየው የአማርኛ አጻጻፍ ስልቶች በጣም እንደሚያቆስሏት ትናገራለች፡፡
መሰልጠኑ ይሁን መሰይጠኑ በማይገባት ሁኔታ በአንድ ቃል ውስጥ የአማርኛና የእንግሊዝኛ ፊደል ቀላቅሎ መጠቀም (ZEናጭ) ለማለት የተፈለገው ‹‹ዘናጭ›› ተቀላቅሎ መጻፍ መጀመሩ ለቁስለቷ ምክንያት ነው ብላ በአብነት ታነሳለች፡፡ ከዚህ ተገቢ ያለሆነ ቅየጣ ወጣቶች እንዲርቁ ትመክራለች፡፡ ልክ እርሷ የማንበብ ፍላጎት እንዳላት ሁሉ ተተኪው ወጣትም ይህን አርአያ ቢከተል የተሻለ ነው ትላለች፡፡ ጸሐፍቱም ቢሆኑ ቢያስተውሉ ስትል አሳስባለች፡፡

አስቴር ኤልያስ

Published in ማህበራዊ

ጥቂት የማይባሉ ሴቶች በልጅነታቸው አልያም በአፍላ ወጣትነት ዕድሜያቸው በሚያምኗቸውና የቅርቤ በሚሏቸው ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም በአሠሪዎቻቸው አማካይነት ይደፈራሉ፡፡ በጣም ጥቂቶቹ ደግሞ ክፉ አጋጣሚ ገጥሟቸው በማያቁት ሰው የመደፈር አደጋ ይደርስባቸዋል። ይህንን ተከትሎም ያለተፈለገ እርግዝና ይከሰታል፤ ያኔ ጭንቅ ጥብ ይሆናል፡፡ ወዲህ የዕድሜ ትንሽነት አለ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ተላላፊ በሽታ ይይዘኝ ይሆን የሚል ስጋት ይጋረጣል፡፡ 

ብዙዎቹ ‹‹ሠርተን እንለወጣለን፤ ቤተሰባችንንም እንደግፋለን›› ብለው አካባቢ የሚወጡም ናቸውና ይህንን ጉድ ይዘው ወደ መጡበት መመለስም የማይታሰብ ይሆናል። ስነ ምግባር በጎደላቸው ግለሰቦች ምክንያት በደረሰባቸው የመደፈር አደጋ ያለ ጥፋቱ የሚቀጣውን ጨቅላ ጨምሮ እነሱም ለጎዳና ህይወት መጋለጥ ዕጣ ፋንታቸው ይሆናል። በዚህ መካከል ግን ጥቂቶች ጉዳዩን ወደፍትህ አካላት ለማድረስ በሚወስዱት ቁርጠኛ ውሳኔ የተነሳ የጉዳታቸው ዓይነት ታይቶ ጉዳት አድራሹ በቁጥጥር ስር እንዲውል ይደረጋል፡፡ ቀጥሎም እነርሱም ሆኑ በሆዳቸው የተሸከሙት ጽንስ ማረፊያ ያገኙ ዘንድ ለዚሁ ተብሎ በበጎ ፈቃደኛዋ ወይዘሮ ወደ ተቋቋመው የሴቶች ማረፊያና ልማት ማህበር የመምጣት ዕድል ያገኛሉ።
ማህበሩ፣ ሴቶቹን ለደህንነታቸው አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ብሎም ምቾት ተሰምቷቸው የደረሰባቸው ጉዳት ይሸር ዘንድ አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ ለነገ ብቁ ዜጋ ይሆኑ ዘንድም በተለያየ መልኩ ያዘጋጅላቸዋል። በቪላ ቤቶች መካከል ያለው ትልቁ ቤትም ሥራው ይኸው ነው። ማህበሩ ለእነዚህ ጉዳት ለደረሰባቸው ሴቶች ከለላን ይሰጥ ዘንድ የተዘጋጀው ግቢ ደጃፍ ሲከፈት በርካታ ሴቶችና ሕፃናት ይታያሉ። ገሚሶቹ ልጆቻቸውን ያጠባሉ፤ ሌሎቹ ክብ ክብ ሠርተው ያወጋሉ፡፡ ሕፃናቱ እዚህም እዚያም በራሳቸው መንገድ ይጫወታሉ፤ በግቢው ወስጥ ከሰባ ያላነሱ ወጣት ሴቶች ከልጆቻቸው ጋር ተጠልለዋል፡፡ መጠለል ብቻም አይደለም፤ የተለያዩ የሙያ ስልጠናዎችን ያገኛሉ፤ ራሳቸውንም ለነገ ህይወት የተሻለ ለማድረግ ያስባሉ።
የሴቶች የኑሮ ውጣ ውረድ ዛሬ የተጀመረ አይደለም፡፡ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሴቶች ሰብዓዊ መብቶቻቸውን ለማስከበር ተቃውሞ የጀመሩበት ወቅት እንደነበር ይታወሳል፡፡ በኢንዱስትሪ በበለፀጉ አገሮች ዘንድ የሠራተኛው ቁጥርና ሥርዓተ ጾታዊ ስብጥር በከፍተኛ ደረጃ ሚዛናዊ ያልነበረ ከመሆኑ የተነሣ በአብዛኛው በጣም ትንሽ የሚሆኑት የኢንዱስትሪው ሴት ሠራተኞች እአአ ለ1910ሩ ታሪካዊ ኮንፈረንሰ ቅድመ ሁኔታ መሟላት ምክንያት ነበሩ፡፡ በተለይም በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችና በማምረቻ ቦታዎች የሚሠሩ ሴት ሠራተኞች ለጤና በማይስማማ የሥራ ቦታ ከመመደባቸውም በላይ እጅግ አነስተኛና የዕለት ኑሯቸውን ለመምራት በማያስችላቸው ክፍያ ይሠቃዩም ነበር፡፡
በዚህም ምክንያት ደግሞ የሴት ሠራተኞችና ተባባሪ ወንድ አጋሮቻቸው በሚያደርጉት አመጽ በኢንዱስትሪው እንቅስቃሴ ላይ ተደጋጋሚ የሆነ ኪሣራ መድረሱ እየተባባሰ ሄደ፡፡ ታዲያ በዚያን ዘመን ከሴቶች ጎን በመቆም አመጽ ያነሱት ወንዶች ዛሬ ላይ ‹‹ወንዶቹን ምን ነካቸው›› በሚያስብል ደረጃ የተለያዩ በደሎችን በእህቶቻቸው ላይ እያደረሱ ስለመሆኑ ደግሞ ቀደም ብለን ባነሳነው ትልቁ ቤት ውስጥ ተጠልለው ያሉት ሴቶች እማኞቻቸን ናቸው። ለእነዚህ ሴቶች ደግሞ ማረፊያና ልማት ማህበሩ እናትም አባትም ሆኖ እራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የወለዷቸውንም ልጆቻቸው ሁሉ ድጋፍና ከለላ በመሆን 12 ዓመታትን አስቆጥሯል።
ከሰባ ያላነሱ ሴቶችን ከልጆቻቸው ጋር አስጠልሎ ከጥቃት እየጠበቀ ብሎም ከደረሰባቸው ወይም ካሳለፉት መጥፎ ታሪካቸው ያገግሙ ዘንድም የተለያዩ የስነ ልቦና ምክሮችን እንዲያገኙ እያደረገ «ነገም ሌላ ቀን ነው» ብለው እንዲያስቡ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራትንም እያከናወነ ይገኛል፡፡ ይህንንም ተግባሩን በቦታው ተገኝተን በዓይናችን ተመልክተናል ።
ማህበሩ አስጠልሏቸው ከሚገኙ ወጣት ሴቶች መካከል ደግሞ በእህቷ ባል የመደፈር አደጋ የደረሰባት ሂክማ አህመድ ትገኝበታለች። ሂክማ የመደፈር አደጋ ቢደርስባትም የእህቷን ትዳር ላለመበጥበጥ ብሎም የጥቃት አድራሹን ዛቻ በመፍራት ጉዳቷን በሆዷ ይዛ የ8ኛ ክፍል ትምህርቷን ለመማር ጥረት አደረገች። ሆኖም የደረሰባት ወንጀል አስከትሎት የመጣውና ሊደበቅ የማይችለው እርግዝና ግን ሁሉንም ፍርጥርጥ አደረገው። በዚህም በቀድሞ ሁኔታ ከአህቷ ጋር መኖር አልቻለችም። ሂክማ የዛሬ ዓመት ከአራት ወር አካባቢ በፖሊስ አማካይነት የሰባት ወር ነፍሰጡር ሆና ወደ ማህበሩ መጣች።
«ጥቃቱ የደረሰብኝ በእህቴ ባል ነው። ጥቃቱ ሲደርስብኝም ልጅነቴ ተደምሮበት ምንም አላውቅም ነበር። ሆኖም ከጥቃቱ በኋላ በተደጋጋሚ ያመኝ ስለነበር በእህቴ አማካይነት ወደ ጤና ጣቢያ ሄጄ በመመርመሬ የሰባት ወር ነፍሰ ጡር መሆኔን አወቅሁ» ትላለች።
በሆነው ነገርም እህቷን ጨምሮ እሷም ችግር ላይ ወደቁ፤ ሰውየውም ማስፈራራቱን ቀጠለ፤ ሆኖም በተለይም ከጤና ጣቢያ ወደ ጋንዲ ሆስፒታል ሪፈር በተባለችበት ወቅት ችግሯ ታወቀ፡፡ ሆስፒታሉ ጉዳዩን ፖሊስ እንዲይዘው በማድረጉና ሂክማም ወደ ማህበሩ መጥታ ማረፊያ እንድታገኝ መሆኑን ነው ወጣቷ ያስረዳችው።
«እህቴ፣ ጥቃት ያደረሰብኝ ባለቤቷ መሆኑ ስታውቅ ከፍተኛ የሆነ መደናገጥን ፈጥሮባት ታማም ነበር፤ በዚህ ሁኔታ ደግሞ አብሬያት መኖር አልቻልኩም፡፡ ግን ግራ በተጋባሁበት ወቅት ፖሊስ ወደ ሴቶች ማረፊያና ልማት ማህበር አመጣኝ፤ በዚህም ወንድ ልጅ በሰላም ተገላገልኩ» ስትል ያሳለፈችውን ህይወት ትናገራለች።
ዛሬ ላይ ባገኘችው ከለላና ድጋፍ ልጇን ወልዳ በማሳደግ ላይ ከመሆኗም በላይ በጸጉር ሥራ ሙያ ሠልጥና ተመርቃለች። አሁን ደግሞ ልብስ ስፌት እየተማረች ነው። ‹‹ከቤተሰቤ ጋር ብኖርም እንደዚህ የሚመቸኝ አይመስለኝም›› የምትለው ሂክማ፣ በተለይም ከመውለዷ በፊት የነበራት ተስፋ መቁረጥ ተወግዶላት ሁሉም ችግር በጊዜው ያልፋል ነገም ሌላ ቀን ነው በማለት እየኖረች እንደምትገኝም ነው ያብራራችው።
በሰው ቤት ሠራተኝነት ትኖር የነበረችው ሊዲያ ቃሉም በአሠሪዋ ወንድም የመደፈር አደጋ የደረሰባት ናት። እርሷም እንደ ሂክማ ሁሉ ወደ ማህበሩ ስትመጣ ነፍሰ ጡር ነበረች፡፡ ዛሬ ላይም ልጇ ተወልዶ የሦስት ወር ዕድሜን አስቆጥሯል። ሊዲያ በማህበሩ በቆየችባቸው ስድስት ወይንም ሰባት ወራት በተሰጧት የተለያዩ የስነ ልቦና ድጋፎች በአሁኑ ወቅት ከጉዳቷ አገግማ ነገን በተሻለ ሁኔታ ለመኖር እንድታቅድ አስችሏታል፡፡
‹‹እኔን መሰል ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች በተቻለ መጠን ጉዳታቸውን አይደብቁ፡፡ ቢችሉ ለሚቀርቡት ሰው፣ ካልሆነም ወደ ህግ አካል በመሄድ ጉዳታቸውን ይናገሩ። አፍኖ መኖሩ ጉዳት እንጂ ጥቅም የለውም›› ባይ ናት።
የሴቶች ማረፊያና ልማት ማህበር መሥራችና ዳይሬክተር ወይዘሮ ማሪያ ሙኒር እንደሚሉት፤ ማህበሩ ስሙ እንደሚያስረዳው በተለያዩ ሁኔታዎች ጥቃት የደረሰባቸውንና የትም መሄድ ለማይችሉ ሴቶች ማረፊያ መስጠት ነው፡፡ ማረፊያ አግኝተው ከመቀመጥ ባሻገር አምራች እንዲሆኑም የተለያዩ ስልጠናዎችን ይሰጣቸዋል።
እንደ ወይዘሮ ማሪያ ገለጻ፤ ሴቶች ላይ ጉዳት የሚያደርሱት የሚቀርቧቸው የቤተሰብ አባላትን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ናቸው። ከተጎጂዎቹ መካከል ደግሞ አብዛኞቹ በከተማዋ ላይ ምንም ዘመድ የሌላቸው ይሆናሉ፡፡ በዚህም ወቅት ፖሊስ አልያም ሴቶች ጉዳይ ወደ ማህበሩ ይልካቸዋል። ማህበሩም ለእነሱ ታስቦ በተዘጋጀውና በተቻለ መጠን የተጎጂዎችን ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ በሚጠበቅበት ቦታ ላይ የተለያዩ የስነ ልቦናና የሙያ ስልጠናዎችን በመስጠትም እንዲያርፉ ይደረጋል።
በአብዛኛው ወደ ማህበሩ የሚመጡ ሴቶች የመደፈር አደጋ የደረሰባቸው ዕድሜያቸውም ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ናቸው። በርካቶቹም ነፍሰ ጡር ሆነው ነው የሚመጡት። ለእነዚህ ወጣት ሴቶች የህክምናና የምክር አገልግሎት አግኝተውና በሚፈልጉት የስልጠና መስክ ሰልጥነው እንዲሁም ሌሎች ለወደፊት ህይወታቸው ሊያግዟቸው የሚችሉ ነገሮችን አግኝተው እንዲወጡ ይደረጋል። ከነዚህም መካከል መሥራት ለሚፈልጉት የሥራ ዕድል ሲመቻችላቸው ገና በለጋ ዕድሜ ላይ ያሉትንም ቤተሰቦቻቸውን በማፈላለግ እንዲቀላቀሉ የማድረግ ሥራም ይሠራል። በሌላ በኩልም ምንም ዘመድ የሌላቸውና ተማሪ የሆኑት በማረፊያ ቤቱ እየኖሩ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ድረስ እንዲማሩ እየተደረገም ስለመሆኑ ወይዘሮ ማሪያ ያብራራሉ።
ማህበሩ ከዚህ ቀደም ሴቶቹ ለደረሰባቸው ጉዳት በህግ ፍትህን እንዲያገኙ ይሠራ እንደነበር ወይዘሮዋ አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት ግን የተሻሻለው የበጎ አድራጎት ህግ መሰረት ይህ ሥራ ባይፈቀድም ፍርድ ቤት ሲሄዱ አብሮ የመሄድ ብሎም ለፍትህ አካል ሙሉ መረጃን በመስጠት በኩል ምንም ዓይነት ፍርሐት እንዳይሰማቸው የማዘጋጀትና ከኋላ ደጀን በመሆን ከፍተኛ እገዛን እንደሚያደርጉ ይናገራሉ፡፡ በዚህ ሥራም በርካቶች ፍትህ እያገኙ ስለመሆኑም አስረድተዋል።
ማህበሩ፣ ባለፉት 12 ዓመታት ከሕፃናቶች ውጪ ከአራት ሺ በላይ ለሚሆኑ ሴቶች ከለላን ከመስጠቱም በላይ በአዳማና ሐዋሳ ቅርንጫፎችን በመክፈትም ተመሳሳይ አገልግሎትን እየሰጠ ይገኛል። ማህበሩ ይህንን ያህል ሥራ ይሠራ እንጂ በተለይም እነዚህ ጉዳት የደረሰባቸውንና ከፍተኛ የሆነ ከለላን የሚፈልጉ ሴቶችን በቋሚነት የሚያሳርፍበት ቦታ አጥቷል፤ «እኛ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሆነው ችግር በሁሉም ቅርንጫፍ የቤት ኪራይ ነው፤ በተለይም ደግሞ እንደዚህ በርካታ ሴቶችና ሕፃናትን ይዞ ቤት መከራየት ፈታኝ ነው፤ ቤቱ ሲገኝ ደግሞ ከወራት በኋላ ኪራዩ በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል፤ ለማህበሩ የሚሆነው ቤት ደግሞ ከመንገድ ያልራቀ የጸጥታው ሁኔታ አስተማማኝ የሆነ እንዲሁም ሕፃናቱ በመጠኑም ቢሆን ሊጫወቱበት የሚችሉበት ግቢ ሊሆን ይግባል፤ በመሆኑም ይህ ነገር ትኩረት ቢያገኝልን» ሲሉም ይናገራሉ።

እናቶችን ከሞትና ስቃይ መታደግ 

በድል ፍሬ ጤና ጣቢያ ያገኘኋቸው ወይዘሮ ማሪቱ መላኩ በእርጅና ዕድሜ ክልል የሚገኙ አረጋዊት ናቸው። ወደ ጤና ጣቢያው የመጡት በየጊዜው የሚከታተሉትን የደም ግፊት በሽታቸውን ለመታየት ነው። የጤናቸው ሁኔታ ብሎም በጤና ጣቢያው ስላገኙት መስተንግዶ ጠየኳቸው፤ «ዘንድሮማ ምን ችግር አለ? ሁሉም ነገር ያለው በአቅራቢያ ነው፡፡ መታከም ብንፈልግም የምንቸገረው ነገር የለም» አሉኝ።
ጉዳዬ ከሴቶች ጋር የተያያዘ በመሆኑ፤ ይህ ለሴቶች ምን ያህል እየጠቀመ ነው? በሚል አገልግሎቱን አስመልክቶ ጠየኳቸው። «ሴቶች መውለድ ቢፈልጉ፤ የቤተሰብ ምጣኔ ቢያሻቸው፤ ልጆቻቸውን ቢያምባቸው ኧረ! ለሁሉም ነገር ጤና ጣቢያው በየደጃፉ አለ፡፡ በዚያ ላይ በየጤና ጣቢያው ያሉ ወጣት የህክምና ባለሙያዎች ወትሮ ከምናውቀው በተለየ አቀባበላቸውና መስተንግዷቸው ሁሌም በመጣን የሚያሰኝ ነው፡፡ ብቻ አሁን ወቅቱ እንደው የሴቶች ነው ማለት ይቻላል» ሲሉ በአድናቆት በየጤና ጣቢያው ያለውን አገልግሎት አስረዱኝ።
ወይዘሮ ማሪቱ ይህን ቢሉም ቅር የሚያሰኛቸው ነገር መኖሩንም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ በተለይም አሁን ላይ በመላው አገር አስጊ የሆኑት የማይተላለፉ በሽታዎች በተለይ ሴቶችን አብዝቶ የሚያጠቃው እንደካንሰር ያለ ገዳይ በሽታ የሚገባውን ያህል ትኩረት ያለማግኘቱ አሳስቧቸዋል፡፡ ቅድመ ምርመራው ለሁሉም መሰጠት አለበት ካሉ በኋላ፤ መንግሥት ሰፋ ያለ ሥራ ቢሠራ መልካም መሆኑን ይናገራሉ።
ሌላዋ እዚያው በጤና ጣቢያው ያገኘኋቸው ነፍሰጡር ወይዘሮ አሚና ተማም ይባላሉ። ወይዘሮ አሚና አሁን ሁለተኛ ልጃቸውን ለመውለድ እየተዘጋጁ ነው፤ የመጀመሪያ ልጃቸውን በዚሁ ጤና ጣቢያ የህክምና ክትትል በማድረግ ተገልግለዋል፡፡ መስተንግዷቸውም ሆነ አቀባበላቸው እንደሚፈልጉት በመሆኑ በድጋሚ እዚሁ ለመከታተል መወሰናቸውን ይናገራሉ።
በተለይም ዘጠኝ የእርግዝና ወራት ከባድ እንደመሆናቸው፤ የጤና ጣቢያው ሠራተኞች ለነፍሰጡር ሴት የሚያስፈልገውን ክትትል እንዲሁም በየጊዜው የተለያዩ የአመጋገብ፣ ንጽሕና አጠባበቅና መሰል ትምህርቶችን በመስጠት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ስለመሆኑ ነው የሚገልጹት።
«በቀደመው ጊዜ መውለድ ያስፈራ ነበር፡፡ ትልልቅ የመንግሥት ሆስፒታሎች ላይ የሰው ቁጥር ይበዛል፡፡ የባለሙያው መጠን በቂ እና ተመጣጣኝ አይሆንም፡፡ ችግር ቢያጋጥም እንኳን «አልጋ የለም» ስለሚባል በተለይም ለነፍሰጡር ሴቶች ከፍተኛ ችግር ነበር። አሁን ግን በቅርበት ጤና ጣቢያ አለ፡፡ ጤና ጣቢያዎቹ የእናቶችና የሕፃናትን ጤና መሰረት በማድረግ በየአካባቢው በመስፋፋታቸው የወረፋ እና የህክምና አገልግሎቱ የማያሰለች እንዲሁም ርህራሄ የተሞላበት እየሆነ መጥቷል» ባይ ናቸው።
ወይዘሮ ሰላም ደስታ ወደ ጤና ጣቢያው የመጡት ልጃቸውን ለማስከተብ ነው። ወይዘሮ ሰላም ምንም እንኳን ልጃቸውን በጤና ጣቢያ ባይገላገሉም ክትባቱን ወደዚሁ ማዞር መፈለጋቸውን ይናገራሉ። የልጃቸውን የአስር ወር እና የመጨረሻውን ክትባት ማስከተባቸውን የተናገሩት ወይዘሮ ሰላም፤ በእስከ አሁኑ የጤና ጣቢያ ምልልሳቸው ምንም ዓይነት ችግር አላጋጠማቸውም።
በአንዳንድ የግል የህክምና ተቋማትም ክትባቱ አልመጣም፤ በዚህ ቀን አይቻልም፤ በዚያ ቀን ኑ እየተባሉ አለመጉላላታቸውና አለመመላለሳቸውንም ተናግረዋል።
ሴቶች የቤተሰብ ብሎም የአገር መሰረት ናቸው፡፡ በመሆኑም አሁን ላይ በተለይም በጤናው ዘርፍ የተሻለ መስተንግዶ ብሎም አገልግሎት እያገኙ ነው፡፡ ይህም በሚፈለገው ልክ ይመጣ ዘንድ የተጠናከረ ሥራን መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሴቶችና ወጣቶች ዳይሬክተር ወይዘሮ ላምሮት አንዷለም በበኩላቸው እንደሚሉት፤ አገሪቱ የምትከተለው መከላከልን መሰረት ያደረገ የጤና ፖሊሲ ሴቶች በጤናው ዘርፍ ላይ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ብሎም ሁለንተናዊ ጤናቸው ተጠብቆ ከሞት እንዲታደጉ በማድረግ በኩል ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
እንደ ወይዘሮ ላምሮት ገለጻ፤ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ የሴቶችን ጤና በመጠበቅ ረገድ የሚከናወኑ ተግባራት አሉ፡፡ በስነ ተዋልዶ ጤና በኩልም በአግባቡ ተከናውነው ሴቶች ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ በኩል ሰፋፊ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረው፤ ይህም ስኬታማ እንዲሆን ራሳቸውን በልማት ቡድን በመደራጀትና እርስ በእርሳቸውም በመወያየት ለችግሮቻቸው መፍትሔ በማመላከቱ በኩልም ሰፋ ያለ ሥራ መከናወኑን ያብራራሉ።
እነዚህ በመከናወናቸው ደግሞ የመጣውን ለውጥ ሲያስረዱም ዋናው የእናቶችን ሞት መቀነስ መቻሉ ነው፤ ይህም በተለይም እ.ኤ.አ የ2017 ጥናት የሚያመለክተው በአሁኑ ወቅት የእናቶች ሞት በ39 በመቶ መቀነሱ ታይቷል፡፡ በሌላ በኩልም በብዛት ሴቶችን ያጠቁ ከነበሩት ውስጥ ወባና ቲቢን በመሳሰሉት በሽታዎች በኩልም ፖሊሲው በተለይም ነፍሰጡር እናቶችና ሕፃናት ላይ ትኩረት አድርጎ በመሥራቱ በዚህ ረገድም ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን አስረድተዋል።
የማይተላለፍ ሆኖም ሴቶችን ለከፍተኛ የጤና ችግር እየዳረገ ያለው የካንሰር በሽታ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት በኩል ክፍተት አለ በሚል ለቀረበው ሃሳብ፤ በበሽታው የተያዙትን ማከም ብቻ ሳይሆን ፖሊሲው ባስቀመጠው መሰረት የቅድመ መከላከሉን ሥራ ቀዳሚ በማድረግ በተለይም በመውለድ ዕድሜ ክልል ላይ ያሉትን ሴቶች የቅድመ ካንሰር ምርመራ እንዲያካሂዱና ራሳቸውን እንዲያውቁ በማድረግ በኩልም ትላልቅ ሥራዎች ተከናውነዋል። በዚሁ አግባብ መሰረትም ራሳቸውን ያወቁትም ህክምናውን እንዲያገኙ በማድረግ በኩልም ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመሆናቸው ወይዘሮ ላምሮት ይናገራሉ።
በሌላ በኩልም በስነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ እናቶች የቤተሰብ እቅድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ በኩልም በፊት ከነበረበት በአሁኑ ወቅት የ25 በመቶ ጭማሪን አሳይቷል። ይህም በተለይም ራስ በራስ በመውለድና በማሳደግ ምክንያት በሴቶች ላይ የሚፈጠርን የጤና ችግር በማቃለል እንዲሁም የሚወልዱበትን ጊዜ እንዲያቅዱ በማድረግም በኩል ሰፊ ሥራ እየተሠራ በመሆኑ ሴቶችም ተጠቃሚ ሆነዋል።
ሴቶች ነፍሰ ጡር በሚሆኑበት ወቅትም በገጠርም ይሁን በከተማ በጤና ጣቢያ ላይ ነፃ የህክምና ክትትልና የማዋለድ አገልግሎት እንዲያገኙ በተለይም ርህራሄ፣ እንክብካቤና አክብሮት የተሞላበት የጤና ባለሙያ በመፍጠርና ወደ ጤና ጣቢያ በመምጣት አገልግሎቱን እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው። ይህ አገልግሎት ደግሞ በተለይም በገጠሩ አካባቢ የተለየ ገጽታ ያለው በመሆኑና እናቶች ወደ ጤና ጣቢያ ሄደው ልጆቻቸውን እንዳይገላገሉ የሚያደርጓቸው የተለያዩ ድርብርብ ኃላፊነቶች ስላሉባቸው እነሱን የማቃለል፤ ከዚያም ባለፈ የጤና ጣቢያ ቆይታቸው የቤታቸውን ያህል እንዲሰማቸውና እንዲመቻቸው በማድረጉ በኩልም ሰፊ ሥራ መከናወኑን ወይዘሮ ላምሮት ያብራራሉ።
በቀጣይም ሴቶችን አሁን ካለው በተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችን አቅም ለማጎልበት ትልቅ እቅድ ተይዟል፡፡ በሌላ በኩልም ወጣት ሴቶችን በተመለከተ በራስ መተማመናቸውን አጎልብተው የጤናቸውን ሁኔታ መጠበቅ እንዲችሉ በማድረግ በኩል (ስኩል ኸልዝ) የተሰኘ ኢኔሼትቭ አለ፡፡ ይህም ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመፈራረም ወደ ሥራ የመግባት አቅድ መኖሩን ከገለጹ በኋላ፤ ማህበረሰቡ ላይ የሴቶች ተጠቃሚነት የሚጎለብትበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየተሠራ ስለመሆኑ አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት የሴቶችን ጤና ለመጠበቅ ከመሥራት ባሻገር ቀድሞ በታችኛው የሥራ መስክ ላይ የሚታዩትን ሴቶች ከፍ ወዳለውና ወዳልተለመደ የሥራ መስክ በማስገባት በኩል ከፍተኛ ሥራ ተሠርቷል። ይህንንም በደንብ ለማስተካከል በጤና ጥበቃ ስር ባሉ መስሪያ ቤቶች የሥራና የትምህርት ዕድል መመሪያዎች ላይ 30 በመቶው ሴቶች ብቻቸውን እንዲወዳደሩ ከዚያ ውጪ በ70 በመቶ ደግሞ ከወንዶች ጋር እኩል እንዲወዳደሩ በማድረግ አሁንም በ3 በመቶ ቢያንሱ ወይም እኩል ቢሆኑ ቅድሚያ ለሴቶቹ የሚሰጥበት ዕድል አለ። ይህ ደግሞ በሴክተሩ የሴቶችን ተጠቃሚነት ሊያሳይ የሚችል ነው ብለዋል።

እፀገነት አክሊሉ

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ሙሉ በሙሉ በሴቶች የሚመራ በረራን ወደ አርጀንቲና መዲና ቦነስ አይረስ ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ።
አየር መንገዱ የአፍሪካ ሴቶችን ለማበረታታትና የመስሪያ ቤቱ ሠራተኞች ሴት በመሆናቸው ጥሩ አመለካከት እንዲኖራቸው ለማስቻል በማሰብ፤ የሴቶች ቀን አስመልክቶ ቀኑ በሚውልበት የካቲት 29 ሙሉ በሙሉ በሴት የአቪዬሽን ሙያተኞች ተመርቶ ወደ ደቡብ አሜሪካዊቷ አገር አርጀንቲና መዲና ቦነስ አይረስ እንደሚበር ታውቋል።
የአፍሪካ ሴቶችን ያበረታታል የተባለው ይህ በረራ ሴቶች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ ለመሳተፍ የሚያዳግታቸው ምንም ነገር እንደሌለ የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል።
የድርጅቱ ሴት ሠራተኛና ምክትል አብራሪ ቃልኪዳን ግርማ እንደሚናገሩት፤ የእዚህ በረራ ዋነኛ አላማ በረራውን ለሚያካሂዱት ብቻ  ሳይሆን ከዚያ በኋላ ለሚመጡት ሴቶች ብርታት ለመሆንና ማድረግ እንደሚችሉ ለማስተማር ነው።
ሴቶች አልችልም የሚል መንፈስ በውስጣቸው እንዳይፈጠር፣ ወንዶች ማድረግ የሚችሉትን ሴቶችም እንዲሁ እንደሚያደርጉት  ለማሳየት መሆኑንም ገልፀዋል። ጨምረውም ‹‹ እኛን መሆን ለሚፈልግ ሴቶች መስራት እንደሚቻል ለማሳየት ያግዛል።›› ብለዋል፡፡      
እንደምክትል ካፒቴኗ ገለጻ፤ ህልም ያላቸው እንስቶች ህልማቸውን ማሳካት እንደሚችሉና ማንኛውም ሥራ ላይ ሴት በመሆን ምክንያት ሊያደናቀፍ የሚችል ነገር እንደሌለ በረራው ሁነኛ ሚናን ይጫወታል።
በተለይም በረራው በተቋሙ ማንኛውም ሥራ መስክ ላይ የተሰማራችውን ሴት የሚያሳትፍ ስለሆነ የሥራን ክቡርነት እንዲረዱም የሚያግዝ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ3 ሺህ በላይ ሴት ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፤ ከሁለት ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ በሴት አውሮፕላን አብራሪዎችና የበረራ አስተናጋጆች ብቻ የተመራ በረራ ወደ ባንኮክ ታይላንድ ማድረጉ ይታወሳል።


ጽጌረዳ ጫንያለው

Published in የሀገር ውስጥ

ዛሬ የሴቶች ቀን ይከበራል። የሴቶች የአመራርነት ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሴቶች ስልጣን የማግኘትና በኃላፊነት ላይ የመቆየት ሁኔታ እንደሌለ የሚገልፁ አሉ፡፡
በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል መምህርት ዶክተር አልማዝ ባራኪ፤  ሴቶች ወደ ከፍተኛ አመራርነት የሚመጡበት ሁኔታ አድጓል የሚለውን ሃሳብ ይቃወማሉ፡፡ በዚህ በኩል ብዙ ለውጥ እንደሌለ ጠቁመው  አልፎ አልፎ ሴቶች በችሎታቸው ወደ ስልጣን እንደሚወጡ ይናገራሉ፡፡ በኢትዮጵያ በየደረጃው ባሉ የመንግሥት ስልጣኖች ላይ 30 በመቶ ሴቶች መኖር አለባቸው ቢባልም፤ የታሰበው እየሆነ አይደለም ብለዋል፡፡
‹‹በከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች በፕሬዚዳንትነትና ምክትል ፕሬዚዳንትነት እንዲሁም በከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ላይ ያሉት ሴቶች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡›› በማለት፤ በቅርብ የሚያውቁትን ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች እና ህፃናት ቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ኤልያስ ግን ይህንን ሃሳብ ይቃወማሉ፡፡ አንዱ ሰጪ ሌላው ተቀባይ የሚሆንበት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የአመለካከት ችግር ቢኖርም፤ ሴቶችን ወደ አመራርነት በማምጣት በኩል ለውጥ አለ ባይ ናቸው፡፡
ሴቶች አስፈላጊዎቹን መረጃዎችና ሰነዶች በመያዝ ራሳቸውን በማዘጋጀት ለስልጣን በመብቃት በኩል ክፍተት አለባቸው፡፡ የሴቶችን ብቃት በመመስከርና በብቃታቸው ወደ አመራርነት እንዲሄዱ በመደገፍ ረገድ ክፍተት እንደሚስተዋልባቸውም ይናገራሉ፡፡ አብዛኛዎቹ የአመራርነት ቦታዎች በወንዶች ቢያዙም የሴቶች ተሳትፎ ግን ጨምሯል የሚል እምነት አላቸው፡፡
ዶክተር አልማዝ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የሴቶች ወደ ሥልጣን አለመውጣት ብቻ ሳይሆን፤ ወደ ስልጣን ከመጡም በኋላ የሚያስፈልጉ ስልጠናዎችና እገዛዎች አይደረጉላቸውም ይላሉ፡፡ አብረዋቸው የሚሰሩት ወንዶችም ከሴቶች ጋር መስራቱን ምን ያህል ይቀበሉታል? የሚለው ያጠያይቃል ባይ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ሴቶች ይችላሉ ብሎ ተቀብሎ በመተግበር ከላይ እስከ ታች ክፍተት አለ፡፡ ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታይ ችግር ነው፡፡ ለመገናኛ ብዙሃንና ለፖለቲካ ፍጆታ ጥቅም ከማዋል ባለፈ ሴቶች ወደ ስልጣን እንዲመጡ በመስራት ረገድ  ትልቅ ክፍተት እንዳለ ተናግረዋል፡፡ አሜሪካንን ለመምራት ተወዳድረው የተሸነፉትንና ከፍተኛ ብቃት እንዳላቸው የሚናገሩላቸውን ሂላሪ ክሊንተንን በማሳያነት በማቅረብ የችግሩን ዓለም አቀፋዊነት ይጠቁማሉ፡፡ ሴቶች ቦታውን ካገኙ ኃላፊነቱን በብቃት እንደሚወጡ የጀርመኗን መራሄ መንግሥት አንጌላ ሜርክልን ለአብነት ይጠቅሳሉ፡፡
በብዙዎች ዘንድ ሴቶች ከዚህ በላይ መሄድ የለባቸውም ብሎ የመወሰን ሁኔታ አለ፡፡ ይህም እውነታ በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ ደረጃ ይስተዋላል፡፡ ከዶክተር አልማዝ የተለየ ሃሳብ የሚያንፀባርቁት ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ሴቶች ብቃት ካላቸው ተቀባይነትን ማግኘታቸው አይቀርም ባይ ናቸው፡፡ ከተመሪውና ከተወዳዳሪያቸው በአንድና ሁለት ደረጃ ከፍ ብለው መገኘት ከቻሉ ቅቡልነት ይኖራቸዋል ይላሉ፡፡ ከወንድ እኩል ተቀባይነቱ እንዳለ ተናግረው ወሳኙ በልጦ መገኘት ብቻ እንደሆነ ያገነዝባሉ፡፡
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ መምህሩ አቶ ጴጥሮስ ክበበው የሁለቱንም ሃሳብ በከፊል ይጋራሉ፡፡ ሴቶችን ዝቅ አድርጎ የመመልከት አስተሳሰብ መኖሩን ጠቁመው፣ ይህን ለመቀየር ሴቷ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን እንዳለባት ያስረዳሉ፡፡ ሴቷ ለአመራርነት የበቃችውና የምትወዳደረው ባላት አቅም በመሆኑ በራስ መተማመን ስሜት መስራት አለባት፡፡ ብቃቷን ካሳየች ተቀባይነት ማግኘቷ አይቀሬ ነው ብለዋል፡፡
ዶክተር አልማዝ እንደሚሉት፤ ሁሉንም ጎን ለጎን ማስኬድ እንዲችሉ ከተመቻቸ በእርግጥም ከወንዶች በላይ ሴቶች አቅም አላቸው፡፡ ‹‹ሴትን ወደ አመራርነት እናመጣለን›› የሚል ዕምነት ካለ ዕድሉን መፍጠርና ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ አሁን ግን ቀድሞም የተዘረጋ መስመር የለም፡፡
‹‹ሴቶች ሴቶችን ወደ ስልጣን ይሳቡ ቢባል፤ ቀድሞም ስልጣን ላይ ስላልነበሩ አብሮ የመስራቱ ሁኔታ አይኖርም፡፡ በሴት ፕሬዚዳንትነት የሚመራ ዩኒቨርሲቲ በሌለበት አንዷ ሌላኛዋን እንዴት ትስባለች?›› ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡
 ሴቶች በተመደቡበት ቦታና በተሰጣቸው ኃላፊነት ከሙስና ነፃ ሆነው በታማኝነት በማገልገል ረገድ አቻ እንደሌላቸው ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ይገልፃሉ፡፡ ከኪራይ ሰብሳቢነት ነፃ በመሆን እያንዳንዷን ተግባር በአግባቡ ይፈፅማሉ፡፡ ወደ አመራርነት የማምጣት ክፍተት ቢኖርም ስልጣን ካገኙ ውጤታማ መሆናቸውን ያክላሉ፡፡
በትጋት፤ በመንፈሰ ጠንካራነት፤ ችግሮችን ተጋፍጦ በመውጣት፤ ብልሃት ፈጥሮ በማለፍ በኩል ሴቶች የተሻሉ ናቸው፡፡ ከስልጣን ኃላፊነት ባሻገር አልፎ አልፎ የቤት ኃላፊነት ስላለባቸው ህብረተሰቡን ለማርካት ያለውን ጫና አልፎ መሄድ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ ሆኖም ይህን ሁሉ ተቋቁመው ጎልተው የሚወጡ ሴቶች መኖራቸው መዘንጋት እንደሌለበት ያመለክታሉ፡፡
አቶ ጴጥሮስም ይህንን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ ሙስናን ከመዋጋት አንፃር የሴቶች ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በሙስና ተጠርጥራ ዘብጥያ የወረደች ባለስልጣን የለችም፡፡ የአሰራር ሥርዓቱ ባለመቀየሩ ግን ሴቷ ሃቅኝነቷን ተጠቅማ ለውጥ እንድታመጣ አልተደረገም፡፡ ጫናዎች የሚቀነሱበት ሁኔታ በስፋት የለም፡፡   ሥልጣን በጥቅሻና በፉጨት በአብዛኛው ለወንዶች መሰጠቱ  ዋናው ችግር ነው ብለዋል፡፡
ሴቶች ታማኞች፣ ሌላው በሰራው ሪፖርት ተኩራርተው እዩኝ እዩኝ እንደማይሉ የጠቆሙት ዶክተር አልማዝም፤ ባልሰሩት ሥራ ራሳቸውን አይሸጡም ብለዋል፡፡ ‹‹ኮታ የሚባለውን ነገር አልደግፍም፡፡  በጥሰው ሊወጡ የሚችሉ አቅም ያላቸው ሴቶች መኖራቸውን አምናለሁ፡፡ ያለአቅማቸው በኮታ መጥተው አይችሉም መባልም የለበትም››ይላሉ፡፡ አቅም ሳትፈጥር ወደ ስልጣን የመጣች ሴት ኩርኩም ሲበዛባት እንደምትጠፋ ያስረዳሉ፡፡ ስለሆነም ብቃት ያላቸው እንዲወጡ ማመቻቸት ይገባል የሚል ዕምነት አላቸው፡፡   
የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት፣ የሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር፣ የክልል ፕሬዚዳንት፣ የከተማ ከንቲባ፣ የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪነት ሳይቀር ከ99 በመቶ ያላነሰው በወንዶች መያዙ ብቃት ያላቸው ሴቶችን ለማምጣት የሚያስችል የአሰራር ስርዓት ባለመፍጠሩ   ነው ብለዋል፡፡ ዋናው መፍትሄም የአሰራር ስርዓቱን ማስተካከል እንደሆነ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ተናግረዋል፡፡  
አቶ ጴጥሮስ መገናኛ ብዙሃን በዚህ በኩል በተከታታይ በመስራት ለውጥ ማምጣት እንዳለባቸው ያምናሉ፡፡ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በየዓመቱ ከየትምህርት ክፍሉ  ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የሚመረቁ ሴት ተማሪዎችን ያስቀራል፡፡ ይህን ተሞክሮ ሌሎቹም ሊጋሩት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡
ከ193 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ሀገራት መካከል፤ ከአስር በመቶ በታች በሚሆኑ አገራት ሴቶች በመሪነት ቦታ ላይ እንደሚገኙ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በኢትዮጵያ በንጉሡ ዘመን ከ240 የፓርላማ አባላት 2 ሴቶች፤ ከ835 የደርግ የሸንጎ አባላት 14ቱ ሴቶች ሲሆኑ፤ በኢህአዴግ ዘመን ሴት የፓርላማ አባላት 30 በመቶውን ይዘዋል።
በዓለም ለሚታየው መመሰቃቀል ለሴቶች ትክክለኛው ቦታ አለመሰጠቱ በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡ ከእያንዳንዱ ጠንካራ መሪ ጀርባ ጠንካራ ሴቶች ቢኖሩም የወንዶችና የሴቶች ስልጣን አልተመጣጠነም፡፡ ሴቶች ለህብረተሰቡ ቅርብ በመሆናቸው ወደ ስልጣን ቢመጡ የህዝቡን ችግር ለማቃለል ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በአገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአሰራር ስርዓትንና አመለካከትን በመቀየር ብቃት ያላት ሴት በትክክል ወደ ስልጣን ከመጣች ተዓምር መፍጠር ይቻላል፡፡ ሙስናን ከመቀነስና ከመከላከል በተጨማሪ መጪውን ጊዜ ብሩህ ማድረግ እንደሚቻልም አስተያየት ሰጪዎቹ ያምናሉ፡፡

ዜና ትንታኔ
ምህረት ሞገስ
 

Published in የሀገር ውስጥ

ወይዘሮ ደሚቱ ሀምቢሳ ተወልደው ያደጉት በምዕራብ ወለጋ ጉኒሾ ቴጌ ቀበሌ በምትባል መንደር ነው። ከአርሶ አደር ቤተሰብ የተገኙት የዛሬዋ ሚኒስትር ተወልደው ባደጉበት አካባቢ በወቅቱ ‹‹ሚሽኖች›› የሚኖሩበት ቦታ ስለሆነ ትምህርት ቤት ለማግኘትና ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ ችግር አልገጠማቸውም። በመሆኑም በልጅነታቸው «ሀሁ...» ብለው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አቅራቢያቸው ተምረዋል። ከዚያም በአዳሪ ትምህርት ቤት በመግባት እስከ 12ኛ ክፍል ተምረዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ዩኒቨርሲቲ በመግባትም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኬሚስትሪ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። በተማሩት የትምህርት ሙያም መምህርት በመሆን አገልግለዋል። ሆኖም ግን በዚህ አላቆሙም በድጋሚ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በህግ ለሁለተኛ ጊዜ የዲግሪ ባለቤት ሆነዋል። በተማሩበት በዚሁ ሙያም በኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ አገልግለዋል። እንዲሁም በኢንተርናሽናል ሊደር ሽፕ ግሪንዊች ኮላብሮሺን ዊዝ አዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ በሚሰጠው የትምህርት ዕድል ተቋዳሽ በመሆን በሊደር ሽፕ የማስተርስ ዲግሪ ማግኘታቸውን ይናገራሉ። 

በአርሶ አደር ቤተሰብ ውስጥ ያደጉት ወይዘሮ ደሚቱ ቤተሰቦቻቸው ያልተማሩ ቢሆኑም ልጃቸው ግን እንድትማርና ለትልቅ ደረጃ እንድትበቃ ትልቅ እገዛ አድርገዋል። « በተለይ አባቴ ለእኔ ትምህርት መሰረት ነው። ይደግፉኛል» በማለት የአባታቸውን ውለታ ደጋግመው ያነሳሉ። የወላጆቻቸው ጥረት የእርሳቸውም ትጋት ታክሎበት ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ እንዳበቃቸው በመጥቀስ።

የሥራ ላይ ቆይታ
ወይዘሮ ደሚቱ ትውልድ ቀራጭ መምህርት ሆነው ሠርተዋል። የትምህርት ቢሮም ኃላፊ ሆነዋል። ወደ ክልሉ መስተዳድር ከመጡም በኋላ የክልሉ አፈጉባኤ እንዲሁም የክልሉን ፍትህ ቢሮም አገልግለዋል። በእነዚህ ሁሉ በቆዩባቸው የሥራ ላይ ኃላፊነቶች ስኬታማ መሆናቸውን ይናገራሉ።
በአገራችን የሴት ሚኒስትር ብዙም የተለመደ አይደለም። ጠንካራ የፖለቲካ ተሳትፎም ቢሆን አነስተኛ ነው። በመሆኑም በጣት ከሚቆጠሩ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ሴቶች መካከል አንዷ በመሆን ሦስት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን በሚኒስትርነት መርተዋል። ይሄውም በፌዴራል ደረጃ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው ለሦስት ዓመታት ሠርተዋል። የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል። አሁንም ላለፉት ሁለት ዓመታት የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። በዚህ ሁሉ ተቋማት ሲሠሩ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫና ዕቅድ ላይ የራሳቸውን ክህሎት ጨምረው የድርሻቸውን በመወጣት ውጤትም ያስመዘገቡበት እንደነበር ይጠቅሳሉ።
የቤተሰብ ሁኔታ
የሴቶች ኃላፊነት ድርብርብ ነው። በተለይ ልጆች ወልዶ ማሳደግ፣ ለቁም ነገር ማብቃት ትልቁ የሴቶች ሥራ ነው። እሳቸውም በዚህም በኩል ውጤታማ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። «ሁለት ልጆች አሉኝ። አንድ ወንድ እና አንድት ሴት። ሁለቱም የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ጨርሰው አሁን የመንግሥት ሠራተኞች ናቸው። አስተምሬም ድሬያቸዋለሁ፤ አሁን የራሳቸውን ህይወት እየመሩ ይገኛሉ። በራሴ መንገድ እንዲቀረፁ በማድረጌ ስኬታማ ለመሆን ችለዋል። ስለዚህ በልጆች ማሳደግም ሆነ በየደረጃው የተጣለብኝን ኃላፊነት በመወጣት አንፃር ስኬታማ ነበርኩ» በማለት ይናገራሉ። ለስኬታቸው ታዲያ ምስጢሩ ምን ይሆን?
ሴትነትና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት
ሴቶች ኃላፊነትን መሸከም የሚችሉ፣ ታማኝ፣ ጠንካራ፣ የዓላማ ፅናት ያላቸው ታታሪም ናቸው። በተሰጣቸው የሥራ ኃላፊነት በብቃት ሲወጡ ይታያሉ። ወይዘሮ ደሚቱም ከእነዚህ ሴቶች አንዷና ለሌሎች አርአያ የሚሆኑ ናቸው። የሴትነት ጉዳዮችንና ሌሎች የሥራ ኃላፊነቶችን እንዴት አድርገው እንደሚያጣጥሙ እንዲህ ሲሉ ይነግሩናል።
«ዋናው ነገር ራስን በፕሮግራም ማስተዳደር መቻል ነው። ሴት ላይ ሥራ ይበዛል፤ የቤት ውስጥ ሥራ፣ ቤተሰብን መንከባከብ ፣ማህበራዊ ጉዳዮች፣ በቢሮ ደግሞ ሥራና ኃላፊነት አለ። ስለዚህ ይሄንን ሁሉ አጣጥሞ መሄድ ያስፈልጋል። ሥራን በዕቅድ መምራት ከተቻለ ሁለቱንም ጎን ለጎን ማስኬድ ይቻላል። በእኔ በኩል ሁለቱን ኃላፊነቶች አጣጥሞ በመሄድ በኩል ምንም የገጠመኝ ችግር የለም። ቤተሰብ በማስተዳደሬ ከአመራርነት ያጓደልኩት ነገር የለም። አመራር በመሆኔም ለቤተሰቦቼ ያጎደልኩት የለም። ዋና ነገር ሁሉንም ጉዳይ በፕሮግራም ማጣጣም መቻል ነው። ሆኖም ግን የሴቶች ኃላፊነት ድርብ ኃላፊነት በመሆኑ የተለያዩ ፈተናዎች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ይጠበቃል።
ወንዱ በቤት ውስጥ የሚጠበቅበት ሥራ የለም። ካለም የሴቶችን ያህል አይሆንም። እኛ ግን ልጆችን ማስተዳደር፣ ማስጠናት፣ ቤተሰቡን መንከባከብ ግዴታችን ነው ብለን ወስደናል። በቢሮ ያለውን ደግሞ መምራት እንደ ቢሮ ኃላፊ ደርበን የምንሠራው ሥራ ነው። ዋናው ግን ሥራን በፕሮግራም መምራት ከተቻለ፤ እችላለሁ ብሎ በሞራል መሥራት ነው። እኔ በሥራዬ ላይ እችላለሁ የሚል ወኔ አለኝ። ይደክመኛል ብዬ አስቤ አላውቅም። ባለሁበት የሥራ ኃላፊነት ዙሪያ አነባለሁ። ስለዚህ ራስን ማብቃት ማለት ራስን ሁሌ ከንባብ አለመለየት ማለት ነው። ሥራንም በፕሮግራም መሥራት ማለት ነው። የስኬት ምስጢሩ ይሄ ነው።
ሴቶች አንድን ሥራ አሸንፈዋለሁ ብለው በቆራጥነት መነሳሳት፤ራስን አብቅቶ መገኘት ነው የሚያስፈልጋቸው። ነገር ግን ያ ሥራ «ይከብደኛል፤ አልችለውም» የሚል ሰው መጀመሪያውኑ ተሸንፏልና እዚያ ቦታ ላይ ምን ያደርጋል ሲሉ ጥያቄያቸውን በጥያቄ ይመልሳሉ። እችላለሁ ብሎ የሚነሳ ሰው ግን ከራሱም ሆነ ከሌሎች ተሞክሮ እየተማረ ሥራውን በአግባቡ መምራት ይችላል። በዚህ መልኩ እኔንም የፈተነኝ ሥራ የለም። ዋናው ነገር ሥራን በአግባቡ መምራት መቻል ነው። ለሥራ ሞራል የውስጥ ብቃት እንዲኖር ማስቻል ነው። በአሁኑ ወቅት ደግሞ መንግሥት በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ለሴቶች የተለያየ ድጋፍ ይደረጋል። ሴቶች ይበረታታሉ። በዚህ ዕድል ውስጥ ራስን ማብቃት ደግሞ የግለሰቡ መሆን አለበት።
ምክር ለሴቶች
ከሴቶች በላይ ማንም ክህሎት ያለው ሰው የለም ይላሉ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ደሚቱ። ሴቶች ሳይማሩ እንኳን ብዙ የሚሠሯቸው ነገሮች እንዷላቸው በማስታወስ። ሴቶች ሁሌም ይችላሉ ባይ ናቸው። በገጠር የምትኖርን ሴት በምሳሌነት ያነሳሉ። በቆሎ ፈትጋ፣ ፈጭታና እንጀራ ጋግራ ማቅረብ የምትችል ናት። ጠላ ጌሾና ብቅል አመጣጥናና ጠምቃ የምታቀርብ ናት። ሌሎችንም ምግቦችና መጠጦች አመጣጥና ቀምማና አጣፍጣ ትሠራለች። ይሄንን የሚያደርጉ ያልተማሩት እናቶች ናቸው። ይህንን ማድረግ የቻሉ ያልተማሩ ሴቶች እንዳሉት ሁሉ የተማሩት ሴቶች ደግሞ ገና ከመጀመሪያው አልችልም ሳይሆን እችላለሁ ብሎ የራስን ብቃት በሥራ መፈተሽ ይገባል። ለተመደቡበት ቦታ ብቁ ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል። ለዚያ ደግሞ ራስን ማብቃት በዕቅድ መምራት ይገባል። ለዚህ ደግሞ በመጀመሪያ ደረጃ ሴቶች ዕድሉን እንድናገኝ መጣርና መታገል አለብን። ዕድሉን ካገኘን ደግሞ በዚያ ውስጥ መብቃት በራስ መተማመን ነው። የአቅም ጉዳይ በሥራ ውስጥ የሚመጣ ነው። ስለዚህ ሴቶች ያለንን ዕምቅ አቅም አውጥተን ሥራ ላይ ማዋል የምንችለው ወኔ ሰንቀን ስንሠራ ብቻ ነው። ዋናው እንችላለን ብለው ራሳቸውን አብቅተው መምራት መቻል ነው።
ቀጣዩ ዕቅድ
የዛሬዋ ሚኒስትር ነገ ደግሞ አሁን ካሉበት በተሻለ (በበለጠ) የኃላፊነት ቦታ ላይ ራሳቸውን የማግኘት ምኞት አላቸው። የነገው የእግዚአብሄር ፈቃድ ነው። ነገር ግን አሁን ካለሁበት በላይ መንግሥት ኃላፊነት ቢሰጠኝ አልችልም ብዬ አልመለስም። እስከአሁንም አልችልም ብዬ አላውቅም፤ እችላለሁ። ዋናው ጉዳይ ቦታው ለሚጠይቀው ክህሎቱ ካለ፣ በእኔ ስንፍና የሚቀር ነገር አይኖርም። ስለዚህ የሚያስፈልገው እችላለሁ የሚል የውስጥ ብቃት ብቻ ነው።
በአገሪቱ አለ የሚባለውን ከፍተኛ የሥልጣን ደረጃ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ቢሰጣቸው ይቀበላሉ? ለሚለው ጥያቄ «ቢሰጠኝ እወጣዋለሁ» በማለት በድፍረትና በወኔ ነበር ምላሻቸው። እኛም የመጀመሪያዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ልንላቸው መልካሙን ተመኘን። በሴቶች ተጠቃሚነትና ቀጣይ አቅጣጫ ዙርያ የአነሱትን ሃሳብ ደግሞ እንደሚከተለው ነው፡፡
የሴቶች ተጠቃሚነት
ወይዘሮ ደሚቱ እንዳሉት ሴቶች በህገ መንግሥቱ በተሰጣቸው መብት በፖለቲካ፣ በማህበራዊ እና በኢኮኖሚው ዘርፍ ተጠቃሚ ሆነዋል። በኢኮኖሚው ዘርፍ ሴቶች በህገ መንግሥቱ ተጠቃሚ የሆኑት አንዱ በመሬት ባለቤትነት መብት ነው። የመሬት ባለቤትነት መብታቸውን በማረጋገጥ ከአጋራቸው ጋር በጋራ ካርታ ( የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፍኬት) የወሰዱ አሉ። እማወራዎቹም በራሳቸው በመሬታቸው ላይ የመሬት ባለቤትነት ካርታ ወስደዋል። ሌላው ንብረት ማስተዳደር፣ ማስተላለፍና ቋሚ ንብረት ማፍራት በህገ መንግሥቱ ያገኙት መብት ነውና ሴቶች በኢኮኖሚው ተጠቃሚ ሆነዋል።
እንዲሁም ሴቶች ተደራጅተው የኢኮኖሚ አቅማቸውን ማጠናከር እንዲችሉ የሚያደርግ ፖሊሲና ስትራተጂ ተቀምጧል። በተለይ በጥቃቅንና አነስተኛ፣ በሙያ ማህበር፣ በፆታ ማህበር ተደራጅተው የራሳቸውን የኢኮኖሚ ችግር እያቃላሉ ያሉበት ሁኔታ አለ። የሴት ደራሲያን ማህበር፣ መምህራን ማህበር ፣ በሙያ ማህበር ሴቶች ተደራጅተው እንዲጠቀሙ በተሰጣቸው መብት መሰረት ተደራጅተው ያቋቋሙትና ተጠቃሚ የሆኑበት ነው።
በማህበራዊ ዘርፍም ሴቶች በተለያየ ትምህርት ተሳትፏቸው የተጠናከረ ነው። የአንደኛ ደረጃ ተሳትፏቸው ከወንዶች እኩል ነው። በሁለተኛ ደረጃም የተሻለ ተሳትፎ አላቸው። ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲደርሱ እየቀነሱ የሚመጡበት ሁኔታ አለ። ምንድነው ማነቆው የሚለው ትልቁ ችግር ተለይቶ እየተሠራ ይገኛል። ሴቶች ከታች ጀምሮ ለቤተሰብ ኃላፊነት ስለሚዳረጉ ለጥናት ያላቸው ጊዜ በጣም ጠባብ ነው። ስለዚህ ሊደገፉ ይገባል ተብሎ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ የማጠናከሪያ ትምህርት ተመቻችቶላቸው ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ሴቶች ሳይባረሩ እንዲቀጥሉ ምቹ ሁኔታ የተፈጠረበት ሁኔታ አለ። በዚህ ዕድል ተጠቅመው ጥሩ ደረጃ ላይ የደረሱ ሴቶች አሉ። ሆኖም ግን አሁንም ከዩኒቨርሲቲ የሚያቋርጡ ሴቶች እንዳይኖሩ ነው እየተሠራ የሚገኘው።
በጤና ዙሪያም ሴቶች በአቅራቢያቸው የጤና ተቋማት ልዩ ልዩ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል። የእናቶችና ሕፃናት ሞትን በመቀነሱ ዙሪያ ሰፊ ሥራ ተሠርቷል። እናቶች በጤና ተቋማት በመውለዳቸው የእናቶች ሞት ቀንሷል። በእርግዝና ወቅት ከወሊድ በፊትና በኋላ የጤና ተቋማት አገልግሎት እንዲያገኙ የጤና ተቋማት ፓኬጅ ተቀርፆ ነው ያለው። ይሁን እንጂ ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አንፃር አሁንም በደንብ መሥራት ይጠይቃል።
ከጤና ጋር ተያይዞ እናቶች የጡት እና የማህፀን ጫፍ ካንሰር እንዲሁም የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ምርመራ እንዲያደርጉና ሙሉ የጤና ፓኬጅ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በየደረጃው ያሉ የጤና ተቋማት በዚህ ዙሪያ ሁሉም ቦታዎች ዝግጅቶች አድርገዋል። ይህንን አገልግሎት እናቶች የሚያገኙት በነፃ ነው። በዋነኛነት ግን እናቶች ወደ ጤና ተቋም ከመሄድ የሚቆጠቡት ከክፍያ ጋር በተያያዘ ብቻ አይደለም። ትልቁ ችግር የግንዛቤ ማጣት ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በጤና ተቋማት ሲሄዱ የተፋጠነ አገልግሎት ማጣት ነው። ስለዚህ ይሄንን ችግር በጋራ መከላከል ያስፈልጋል።
በፖለቲካ ዘርፍም ሴቶች በውሳኔ ሰጪነት ላይ መሳተፍ ችለዋል። በምክር ቤቶች ደረጃ አሁን የሴቶች ቁጥር በጣም ጨምሯል። ለምሳሌ ቀደም ሲል ሁለት በመቶ የነበረው የሴቶች ቁጥር አሁን ወደ 38 ነጥብ 8 በመቶ ደርሰናል። በአጠቃላይ የሴቶች ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል። ግን ደግሞ በተፈለገው መጠን ፍጥነቱና ብዛቱ የደረሰበት ደረጃ ሲታይ አሁንም ገና ብዙ ሥራ መሥራትን ይጠይቃል። በተለይ ደግሞ የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አመለካከት፣ ሴቶች ለራሳቸው ያላቸው የበታችነት ስሜት እና ማህበረሰቡም ሴቶችን አሳንሶ የማየትና አይችሉም የሚለውን አመለካከት የመቅረፍ ሥራ በደንብ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ስላወገዝን ብቻ አይጠፋም። የኢኮኖሚ አቅም ሲጠናከር ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ይጠፋሉ ብዬ አስባለሁ። አንደኛ ሴቶች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል ሀብት ማፍራት ይኖርባቸዋል። የራሳቸው ገቢ ካላቸው የሚደርስባቸውን ጥቃት መከላከል ይችላሉ። ስለዚህ ትልቁ ሴቶችን ቀፍድዶ የያዘው ድህነት ስለሆነ የገቢ ምንጭ እንዲያገኙ ፤ ራሳቸውን እንዲችሉ መደገፍና ማበረታታት ያስፈልጋል። በየጊዜው የህዝብ ንቅናቄና የአመለካከት ለውጥ ለማምጣትና ሴቶች የኢኮኖሚ አቅማቸው እንዲጠናከር ለማስቻል ሴቶች ራሳቸውም ጭምር መሥራት አለባቸው። በሴቶች ላይ ያለ የጎጅ ልማዳዊ ድርጊት አስተሳሰብ የሚቀረፈው ሴቶች በሙሉ አቅማቸው በሁሉም የልማት ሥራ ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ ሲቻልና ሁሉም ርብርብ ሲያደርግ ነው።
በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና ጥቃቶች ሳቢያ የሴቶች የተጠቃሚነት ሁኔታ በሚፈለገው ደረጃ ላይ እንዳይደርስ እንቅፋት እየሆነ ይገኛል። ሴቶች ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊትም ሆነ ከጥቃት ሊጠበቁ፣ የመደራደር አቅማቸው ሊያድግና በራስ የመተማመን መንፈሳቸው ከፍ ሊል የሚችለው በዋነኛነት የኢኮኖሚ አቅማቸው ሲጎለብት እንደሆነ ይታመናል። በመሆኑም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በተለይም ደግሞ የሴት ልጅ ግርዛትንና ያለ ዕድሜ ጋብቻን ሙሉ ለሙሉ ለማስወገድ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ወደ ተግባር ተገብቷል። በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት 1/3ኛ ቀበሌዎችን፣ወረዳዎችንና ዞኖችን ነፃ ለማውጣትና እውቅና ለመስጠት ግብ ተጥሎ እየተሠራ ይገኛል። ለዚህም ውጤታማነት ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ ነው ሚኒስትሯ ያሳሰቡት።
የትኩረት አቅጣጫ
የዘንድሮ አገር አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8) ፕሮግራም ትኩረት የተሰጠው ሴቶች በህብረት ሥራ ማህበራት ተደራጅተው ተጠቃሚ ማድረግ፣ ጠንካራ ቁጠባ ያላቸውን የሴቶች የልማት ቡድኖች ወደ ህብረት ሥራ ማህበራት ማሸጋገር፣ በጤና ፓኬጅ ትግበራ የሴቶችን ተጠቃሚነት በማሳደግ ሴቶች አካባቢያቸውን ንጹህና ለኑሮ ተስማሚ ከማድረግ አኳያ የሚኖራቸውን ተሳትፎ ማጎልበት ላይ ያነጣጣረ ነው።
የሴቶችን አደረጃጀት በማጠናከር ተጠቃሚ ነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ሲሆን፤ ለዚህም ቁጠባ ያልጀመሩትን ወደ ቁጠባ ማስገባት፤ ቁጠባ ጀምረው ያልተጠናከሩትን በማጠናከር ወደ ተሻለ የገቢ ማስገኛ መስኮች እንዲሰማሩ ማድረግ እንዲሁም በህብረት ሥራ እንዲደራጁ ማበረታታትና በተደራጀ አግባብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ነው።
በተጨማሪም በተደራጀ አግባብ በጤና ሙሉ ፓኬጅ ትግበራና በአካባቢ ንጽህና ተሳትፏቸውንና ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ ነው። በአሁኑ ጊዜ በጣም አስፈላጊው የደም ልገሳ መሆኑን ሚኒስትሯ ይናገራሉ። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ከጤና ጥበቃ ጋር ተሳስረን እየሠራን እንገኛለን። ከሌሎች ተቋማት ጋር በጋራ ሥራዎችን እየሠራን ነው። አንዱ ሥራ ከከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ጋር የሚሠራ ሲሆን፤ ይህም አረንጓዴና ፅዱ ከተማ እንዲኖር ማስቻል ነው። በዚህም ችግኞችን የማልማትና ውሃ የማጠጣት ሥራ ይሠራል።« እኔ ደጄንና ቤቴን አፀዳለሁ፤ እርስዎስ» የሚል መሪ ሃሳብ ይዘን አረንጓዴና ፅዱ ከተማ እንድትኖረን በማሰብ እየሠራን ነው።
ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከህብረት ሥራ ማህበራት ኤጀንሲና ከከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ጋር በጋራ እየተሠራ ያለው ሥራ ትልቁና ዋናው የሴቶችን አቅም መገንባት፣ እውቀትና ግንዛቤ እንዲኖራቸውና የጤና ተቋም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ነው። እናቶችም ወደ ጤና ተቋም ሄደው እንዲወልዱ፣ የጡትና የማህፀን ጫፍ የቅድመ ካንሰር ምርመራ እንዲያደርጉ ለማስቻል ነው።
ሌላውና ትልቁ ደግሞ እንደ ሀገር በሰላም፣ በልማትና ዴሞክራሲ ዙሪያ በየመድረኩ ውይይት ሲካሄድ ቆይቷል። ሰላም ከሌለ ልማት የለም፤ ሀገርም የለም። ሰላም ከሁሉም በፊት ቅድሚያ የሚሰጠው በመሆኑ በማርች 8 ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ስለ ሰላም ያላቸውን ግንዛቤ ከፍ ለማድረግና ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የግንዛቤ መፍጠሪያ ተሠርቷል። እነዚህ በሙሉ በቀበሌ፣ በወረዳ እና በዞን ደረጃ የተሠሩ ሥራዎች ናቸው።
በዛሬው ዓለም አቀፍ ሴቶች ቀን በአዲስ አበባ በከተማ ደረጃ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ሴቶች በሚል ማጠቃለያ ውይይት ይደረጋል። በደንብ ቆጥበው ወደ ህብረት ሥራ ማህበር የተሸጋገሩ የሴቶች የልማት ቡድን እውቅና ይሰጣቸዋል። በተለያየ የልማት ሥራ ላይ ተሳትፈው የልማት አርበኛ የሆኑትም የመድረኩ ተሳታፊ ይሆናሉ። ይሄን በማድረግ በሴቶች ዙሪያ ንቅናቄ ለመፍጠር ነው። ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችንም ለማስቀረት የእያንዳንዱ ሰው ግንዛቤ ወሳኝ ነው።

አልማዝ አያሌው

 

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።