Items filtered by date: Friday, 09 March 2018

የስፖርት ጸሐፊያንና የዘርፉ ተመራማሪዎች እንደሚናገሩት፤ የእጅ ኳስ ስፖርት ከእግር ኳስ የቀደመ ጥንታዊ ስፖርት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ስፖርቱ ከጥታዊት ግሪክ ጀምሮ በሮማውያንና ጀርመኖች ዘንድ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በተለይ በመካከለኛው ክፍለ ዘመናት ይዘወተር ነበር፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊትም በአባይ ( ናይል) ጨዋታው ይከናወን እንደነበር የአርኪዮሎጂ ግኝቶች ያመለክታሉ፡፡
የጀርመን የሰውነት ማጎልመሻ መምህራን የሆኑትና ከቤት ውጪ የእጅ ኳስ አባቶች ለመሆን የበቁት ራፋቮልና ኮኒ ግስበርግ ጨዋታዎችን በማስተዋወቅ እንዲሁም ሌላው ጀርመናዊ ሀርቨ ማን እጅ ኳስ እንዲታወቅ ብዙ ጥረት ማድረጉን ታሪክ ያወሳል፡፡ ጨዋታው በጀርመኖች እንደተፈለሰፈ መረጃዎች ቢጠቁሙም እ.አ.አ በ1904 ዴንማርካዊው ሁሉገር ሄልሰን የእጅ ኳስን አስተዋውቋል፤ ደንቦችን አውጥቶም አሳትሟል ይባላል።
የእጅ ኳስ ጨዋታ ዛሬ ላይ ለመድረስ ህጎችን ከማርቀቅ ጀምሮ በርካታ ሂደቶችን ተሻግሯል፡፡ እ.አ.አ መስከረም 13 ቀን 1925 የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ እጅ ኳስ ውድድር በጀርመን እና ኦስትሪያ መካከል ተደርጎ በጀርመን 3ለ0 ተጠናቀቀ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እጅ ኳስ  ዓለም አቀፍ ስፖርት ሆነ።
በኢትዮጵያም 1960 እና 1970ዎቹ እጅግ ተወዳጅና ታዋቂ ጨዋታ ነበር። በ1980ዎቹ ደግሞ ገናና እና በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ሳይቀር ጥሩ ውጤቶችን ማስመዝገብ የተቻለበት የስፖርት ዓይነት ሆነ። የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ክለብም በውጤታማነቱ የናኘ ነበር፡፡ ክለቡ በርካታ ታዋቂና ውጤታማ ተጫዋቾችንም ማፍራት ችሏል። የምድር ባቡር መፍረስን ተከትሎ ግን ስፖርቱ       የኋልዮሽ ጉዞውን ተያያዘው፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በርካቶች እጅ ኳስ ከሌላው የስፖርት ዓይነት ጋር ሲምታታባቸው ይስተዋላል፡፡ አዳዲስ ክለቦችም ዛሬ ተመስርተው በቀጣዩ ቀን እየፈረሱ መምጣታቸውም የተለመደ ሆኗል።
ለመሆኑ አሁን ካለበት ደረጃ ወደየት ያመራ ይሆን? ችግሮቹስ ምንድን ናቸው? በእነዚህና መሰል ጉዳዮች ላይ ዝግጅት ክፍላችን ከኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ፍትህ ወልደሰንበት ጋር ያደረገውን ቆይታ እነሆ!
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ያለው የአገሪቱ የእጅ ኳስ እንቅስቀሴ ምን ይመስላል?
አቶ ፍትህ፡- አሁን የኢትዮጵያ እጅ ኳስ የስፖርቱ ህዳሴ ላይ ነው ማለት እንችላለን፡፡ የምስረታው ታሪክ ረጅም ጊዜ የወሰደ ስፖርት ነበር፡፡ ጠንካራ እንቅስቃሴ የነበረው ሲሆን፤ በመካከል በመዘንጋት ለበርካታ ዓመታት ዓመታዊ ውድድር ብቻ ተካሂዶ የሚቆም ነበር፡፡ ስፖርቱም ለበርካታ ዓመታት ተቀዛቅዞ ቆይቷል፡፡ ሆኖም ይህን ሂደት እንደገና ለማስቀጠል አዲስ ሐሳብ ማመንጨት ተገቢ ሆነ፡፡ በዚህም ስፖርቱን ወደ ህዝብ ለመመለስ፣ የመገናኛ ብዙሃን ትኩረት ለመሳብና የስፖርቱን ወቅታዊ እንቅስቀሴ ለማሳወቅ ሲባል አያሌ ጠቃሚ ተግባራት በትጋት ተከናውነዋል፡፡ ስፖርቱን ወደ ህዝቡ መመለስ በሚል እሳቤ የአፍሪካና ሌሎች ትልልቅ ውድድሮችን ወደ አገር ቤት  እንዲመጡ ተደርጓል፡፡
በዚህ ዕቅድም ከአፍሪካ እጅ ኳስ ኮንፌዴሬሽን ጋር በመወያየት አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካውያን ከተማ በመሆኗ፤ በአገሪቱ ስፖርቱን የሚጋብዙ በርካታ መሰረተ ልማቶች እየተገነቡ መሆኑን በማሳወቅ ብሎም ስፖርቱ ወደ አገራችን እንዲመጣ እንፈልጋለን የሚል ጥያቄ ቀርቧል፡፡ በዚህም መሰረት የዞን ውድድር አዘጋጅነት ለኢትዮጵያ እንዲሰጥ በተጠየቁ ጊዜ ወዲያውኑ ይሁንታውን በመግለጽ የዞን አምስት ‹‹ኤ›› የተባለው ውድድር በአዲስ አበባ ተዘጋጅቷል፡፡ በዚህም ውድድር ኢትዮጵያ በወንዶችም በሴቶችም የዋንጫ ባለቤት ሆናለች፡፡ በተመሳሳይ የመላ አፍሪካ ውድድር ማጣሪያ መርሐግብርም የዞኑን ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ በተጠየቀው መሰረት ይህንንም ማዘጋጀት ተችሏል፡፡ ይህን ተከትሎ የአፍሪካ የወንዶች እና ሴቶችን ውድድር መርሐግብር ማዘጋጀት ተችሎ ነበር፡፡ በዚህ ውድድር ምንም እንኳን በሴቶቹ ስኬታማ ውጤት ባይመዘገብም ኢትዮጵውያን ለመጀመሪያ ጊዜ በወንዶች አራተኛ ወጥታለች፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ እነዚህን ውድድሮች በማዘጋጀቷ ምን ተጠቅማለች?
አቶ ፍትህ፡- በዚህ ውድድር የ11 አገራት ቡድኖች በመምጣታቸው፤ ልምድ ለመለዋወጥ እና የአገሪቱን ገጽታ ለማሳየት ተችሏል፡፡ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድም የራሱን ድርሻ አበርክቶ ነበር፡፡ እነዚህ ሂደቶች ከተከናወኑ በኋላ የተሻለ ሥራ ማከናወን እንደሚቻል ትልቅ ተሞክሮ የተወሰደበት አጋጣሚም ተፈጥሯል፡፡
በሂደቱ በርካታ ስኬታማ ተግባራትና ውጤቶች በመገኘታቸው ስፖርቱ መነቃቃት በመጀመሩ ቀደም ሲል በታሪክ ያልነበረ የኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በ2008 ዓ.ም ተጀምሯል፡፡ በዚህ ወቅትም በስትራቴጂያዊ አሠራር አራት ቦታዎች ማለትም አላማጣ፣ አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ እና ሐዋሳ ተመርጠው በአካባቢው ያሉ ክለቦች ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥረት ተደርጓል፡፡ በእርግጥ በዚህ ወቅት እንደ ክለብ ጠንካራ የነበሩት የፌዴራል ፖሊስ፣ መከላከያ እና የፌዴራል ማረሚያ ቤት ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ክለቦች ጋር በመሆንም ቅድመ ውድድር መርሐግብር ለማካሄድ በተደረገው ጥረት ትልቅ ሥራ ተከናውኗል፡፡ በሂደቱም 15 ክለቦች ማግኘት ተችሏል፡፡
በ2009 ዓ.ም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ፕሪሚየር ሊግ ሲጀመር የጥርጊያ መንገድ የከፈተ ነበር፡፡ ሐዋሳ ላይ ውይይት በማካሄድ ቀደም ሲል የማወዳደሪያ ሥርዓቱ የራሱ ሕገ-ደንቦች ያልነበረው በመሆኑ እንደ አዲስ ደንብም ተበጀለት፡፡ ክለቦቹ አብዛኞቹ አዳዲስ ስለነበሩ የክለብ ማናጅመንት ስልጠና እንዲኖር ተደርጓል፡፡ ይህም ስኬታማ ነበር። ይሁንና የተወሰኑ ክለቦች የፋይናንስ ፈተና ገጥሟቸዋል፡፡ የሆሳዕና እጅ ኳስ ክለብ ግማሽ ላይ አቋርጧል፣ የሐዋሳ እጅ ኳስ ቡድን አቋርጦ የነበረ ሲሆን፤ ኃላፊዎችን በማናገር ወደ ውድድሩ እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡
ሌላኛው የስኬቱ ማሳያ በ2009 ዓ.ም የነበረው የምሥራቅ አፍሪካ ዞን አምስት ውድድር በጅቡቲ አዘጋጅነት ተከናውኖ በወንዶችም በሴቶችም ለሦስተኛ ጊዜ የዋንጫና ወርቅ ባለቤት ሆነናል፤ ለአፍሪካም ውድድር አልፈናል፡፡ የአፍሪካው ውድድር በሴነጋል ተካሂዶ የነበረ ቢሆንም ውጤታማ መሆን ባይቻልም ትልቅ ልምድ ተቀስሞበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የዳኞች ስልጠናም በሰፊው ተከናውኗል፡፡ አዳዲስ ህጎች ላይም ግንዛቤ እንዲኖር ተደርጓል፡፡ ስፖርታዊ ጨዋነት እና የዳኞች ችግር በመኖሩ ተገምግሞ መግባባት ላይ ተደርሶ ማስተካከል እንደሚቻል የጋራ ግንዛቤ ተፈጥሯል፡፡ ዘጠኝ ክለቦች የሚሳተፉበት የ2010 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ እየተካሄደ ያለው የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር ውድድር ተጠናቋል፡፡ በዘንድሮ ጥሩ ውጤት እየተመዘገበ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ፌዴሬሽኑ ከክለቦችና ከክልሎች ጋር ለመሥራት ያለው ተነሳሽነት ምን ይመስላል?
አቶ ፍትህ፡-  ሁሉንም ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ዞረን ለማናገር ሞክረናል፤ ስፖርቱን እስከመርሳት ደረጃ ተደርሶ ነበር፡፡ የክልሎቹ ምላሽም ብዙም አይደለም፤ በእርግጥ በእነርሱም አይፈረድም አንድ አካል ውሳኔ ሲወስን ጥቅሜ ምንድን ነው የሚል እሳቤ አለው፡፡ ስፖርቱ ላይ በሚገባ ባለመሠራቱም በሰፊው አልተዋወቀም፡፡ አሁን ክለቦቹ ያሉት ትግራይ፣ ደቡብ፣ አዲስ አበባ አስተዳደር እና ድሬዳዋ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ሐዋሳ፤ ሆሳዕና እና ባህርዳር ከውድድሩ ወጥተዋል፡፡
በእርግጥ በዚህ ውድድር መሳተፍ ጥልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡ በአንድ ከተማ ብዙ ልማት ተሠርቶ ላይታወቅ ይችላል፡፡ በእነዚህ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ሲካሄዱ ግን በዜና እወጃዎች በደንብ የመታወቅ ዕድል አላቸው፡፡ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከርም ትልቅ ሚና አለው፡፡ ለወጣቶች ብሎም በየዓመቱ ስልጠና ወስደው ወደየቤታቸው ለሚገቡ በርካታ ባለሙያዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ክለቦች በተጠናከሩ ቁጥር ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን እንዲኖር ያስችላል፡፡ በልጅነቱ እጅ ኳስ ተጫውቶ የሚያድግ ታዳጊም ክለብ የመግባትና ውጤታማ የመሆንም ዕድል እንዳለው ይገነዘባል፡፡ በመሆኑም ይህ ሁሉ ፋይዳ እንዳለው በመገንዘብ ሁሉም አካል በመሰረቱ ላይ የጋራ ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ግን በዚህ ዘርፍ ክፍተቶች አሉ፡፡ ክልሎች አካባቢም ገና መሠራት ያለባቸው ተግባራት አሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ባህርዳር፣ ሐዋሳ እና ሆሳዕና ከተማ ከውድድሩ ለምን ወጡ?
አቶ ፍትህ፡- ክለቦቹ ድጋፍ ሳይደረግላቸው በተሳታፊዎቹ ወጪ ነበር ሲጫወቱ የነበረው፡፡ የመጀመሪያ ዓመት ውድድር ላይ ስለነበሩ በቀጣይ ዓመት በጀት ተመድቦ እንደሚወዳደሩ ነበር ፌዴሬሽኑ ከግምት ውስጥ ያስገባው፡፡ ይሁንና ምዝገባ ሲካሄድ ሊመጡ አልቻሉም፡፡ ፌዴሬሽኑ ለምን ቀራችሁ ብሎ በተደጋጋሚ ጠይቋል፡፡ ተጫዋቾቹ ግን በ2009 ዓ.ም ተጫውተን ዘንድሮ ለምን ቀረን ብለው ወደ ፌዴሬሽኑ አልመጡም፡፡ አመራሮችም ጠንካራ ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ውድድሩ መጀመር ስለነበረበት ዘንድሮ በዘጠኝ ቡድኖች  ተጀምሯል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በገንዘብ እጥረት ከውድድሩ የራቁትን ክለቦች ፌዴሬሽኑ በገንዘብ የመርዳት አቅም የለውም?
አቶ ፍትህ፡- ፋይናንሱን በተመለከተ ፌዴሬሽኑ በጣም በችግር ነው የሚያሳልፈው፡፡ ያለፈውን ዓመት ውድድር ለመጨረስ ችግር ስለገጠመው ከግለሰቦች ሳይቀር እገዛ እየተደረገ ነው የተጠናቀቀው፡፡ ለፌዴሬሽኑ ከመንግሥት የሚበጀትለት ከ250ሺ እስከ 300ሺ ብር ነው፡፡ ባለፈው ዓመት የተወሰነ ሥራ በመሠራቱ ለዚህ ዓመት 380ሺ ብር ተበጅቷል፡፡ ግን በዓመት ውስጥ አንድ ሚሊዮን የሚያስወጣ ውድድር ነው የሚካሄደው፡፡ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ዘንድሮ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እንዲያግዝ በመጠየቁ የተቻለውን አግዟል፡፡ ከክለቦችም ጋር በተደረገ ውይይት እያንዳንዳቸው 25ሺ ብር ከፍለዋል፡፡ የቀረው የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ሲሆን፤ እርሱም በቅርቡ ይከፍላል፡፡ በዚህም በጀት ከውድድር በዘለለ ስልጠና ለመስጠትም ታሳቢ ተደርጓል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ባለሀብቶች ‹‹ስፖንሰር›› በማድረግ ስፖርቱን መልክ ሊያበጁለት ይችላሉ፡፡ በዚህ ላይ ምን ያክል ተሠርቷል?
አቶ ፍትህ፡- ለዚሁ ዓላማ ሲባል የባለሙያ ቅጥር ተፈፅሞ፤ ዶክመንቶችም ተዘጋጅተው ነበር፡፡  አቅም ያላቸው አካላትም ‹‹ስፖንሰር›› እንዲያደርጉ ተጠይቀዋል፤ ግን ምንም ምላሽ አልተገኘም፡፡ «ዛሬ ሙሉ ፕሮፖዛል ተሰጥቶ በሌላ ቀን ስንሄድ ከመረብ ኳስ ናችሁ?›› ተብለን እንጠየቃለን፡፡ መገናኛ ብዙሃንም ስፖርቱን በማስተዋወቅ በኩል የተወሰነ ክፍተት አለባቸው፡፡ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ አሁን ግን የታሰበው ነገር አቅም ያላቸውን ሰዎች በአንድ ላይ አሰባስቦ ያለውን ችግር ለመነጋገርና የተሻለ ነገር ለማከናወን በቦርዱ ተወስኗል፡፡ ታዳጊዎችም የሚበራከቱበት አሠራር መዘርጋት ዋነኛው ጉዳያችን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ታዳጊ ስፖርተኞችን መፈለጉ እንዳለ ሆኖ፤ የማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲበራከቱ ምን ተግባራት እየተከናወኑ ነው?
አቶ ፍትህ፡- አሁን ያሉት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ታዳጊዎችን ለማሰልጠን ብዙም አስቸጋሪ አይደሉም፡፡ በክልል ዋና ዋና ከተሞች ደግሞ በርካታ ስታዲየሞች እየተገነቡ ነው፡፡ ይህን ተከትሎም ሁሉንም ውድድሮች አንድ ላይ ለማካሄድ መሰረተ ልማት እያሟሉ ነው፡፡ ይህ ጥሩ ነገር ነው፡፡ እጅ ኳስ፣ ቅርጫት ኳስና መረብ ኳስ ለመጫወት የሚያስችሉ ስፍራዎች አብረው እየተገነቡ በመሆኑ ጥሩ ተስፋ አለ፡፡ ከዚህ ውጪ እንደ ዱራሜ እና አላማጣ አካባቢዎችም ሜዳዎች አሉ፡፡ በከተሞች የማዘውተሪያ ስፍራዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ወደ አገሪቱ እናምጣ ከተባለ አስቸጋሪ ነው፡፡ ደረጃውን የጠበቀ ሜዳ አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ከኢትዮጵያ ስፖርትና ወጣቶች አካዳሚ እና እያረጀ ካለው የአራት ኪሎ ስፖርትና ስልጠና ማዕከል በስተቀር ብዙም የለም፡፡ ምናልባት የአዲሱ ስታዲየም ግንባታ ሲጠናቀቅ መሰል ውድድሮች ሊካሄዱ ስለሚችሉ ተስፋ ይኖራል፡፡
ፌዴሬሽኑ ይህን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ዓለም አቀፉን የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን በማናገር ደረጃቸውን የጠበቁ ሜዳዎች እንዲሆኑ የማንጠፍ ፕሮጀክት ስላላቸው ኢትዮጵያን እንዲያግዙ ተጠይቀዋል፡፡ በመስፈርቱ መሰረትም የሁለት ሜዳዎች ንጣፍ እንዲሠራ ቢመረጥም እነርሱ ግን አንዱን ብቻ ነው በዚህ ዓመት የምንሸፍነው ብለዋል፡፡ ለአንዱ ሜዳ 30ሺ ዶላር ወጪ የሚደረግ ሲሆን፤ ሙሉ ወጪውን ይሸፍናሉ፡፡ ሌሎች የትራንስፖርት ወጪዎችን ደግሞ ባለ ሜዳው ክልል ይሸፍናል፡፡ ይህ ሲከናወን አገሪቱ ደረጃቸውን የጠበቁ የማዘውተሪያ ስፍራዎች ይኖሯታል።
አዲስ ዘመን፡- ታዳጊ ክልሎች የግብዓት አቅርቦት ችግር እንዳለባቸውና ከፌዴሬሽኑ ጋር ቅርበት መስርተው እንደማይሠሩ ይታወቃል፡፡ ዓመታዊ የክልሎች ስፖርት ውድድር ላይም እጅ ኳስ ትኩረት እንደማይሰጠው ይነገራል፡፡ ይህ ለምን ሆነ?
አቶ ፍትህ፡-  ዓመታዊ ውድድሮች በጥሩ ሁኔታ ይካሄዳሉ፡፡ ይሁንና እንደ አፋር እና ጋምቤላ ያሉ ክልሎች ተወዳዳሪዎችን አይልኩም፡፡ ግብዓትን በተመለከተ ዓለም አቀፉ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን እና ዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ኳሶች ይሰጡናል፡፡ ግን በአደረጃጀቱ ክልል ላይ ፌዴሬሽን ለመባል ቢያንስ በውስጡ አምስት ክለቦችን መያዝ አለበት፡፡ ግን እነርሱ ይህን አያሟሉም፡፡ ታዲያ ክልል ይህን ካልሠራ ከፌዴሬሽኑ ጋር በምን አሠራር ተቀናጅቶ ሊሠራ ይችላል? ቢያንስ ለፕሪምየር ሊጉ ክልሎች አንዳንድ ክለብ ቢኖራቸውና ይህን ታሳቢ አድርገው ቢሠሩ የተሻለ ድምቀት ይኖር ነበር፡፡ በመሆኑም ክፍተቱ ያለው እዚያው ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ዓመታዊ ትልልቅ ውድድሮች ሲመጡ ሁሉም ክልሎች እኩል ይጋበዛሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ የፌዴሬሽኑ ባለሙያዎች ባለው በጀት ለመስክ ጉብኝት ሲወጡ ስፖርቱ በጣም አላደገም ተብሎ በሚታሰብ ክልል ነው የሚሄዱት፤ ስፖርቱን ለማበረታት፡፡ ግን በርካታ ክለቦችም ያሉት አዲስ አበባ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስፖርቱን ለማሳደግ የውጭ ዕድሎችን ከመጠቀም በዘለለ ከአገር ውስጥ የስፖርት ትምህርት ከሚሰጡ ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማት ጋር ያለው ቅርርቦሽ ምን ይመስላል?
አቶ ፍትህ፡- እንደ ስትራቴጂ የውጭ ዕድሎችን ወደ አገር ውስጥ እንዲመጡ በማድረግ የተሻለ መነቃቃት ተፈጥሯል፡፡ ነገር ግን በአገር ውስጥ መጠቀም የሚቻለውን አቅም ሙሉ ለሙሉ መጠቀም አልተቻለም፡፡ ለአብነት ያህል ሠልጣኞች ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ውስጥ እስከአሁን አልገቡም፡፡ ግን በየዓመቱ ወደ አካዳሚው የሚገቡ ወጣቶችን ምረጡ ይባላል፡፡ ላለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት ይህ ነገር አልተሳካም፡፡ ስፖርቱ ደክሞ ስለነበር ነው እንዲህ በፍጥነት መንገዱ ያልተመቻቸው፡፡ እስከአሁንም ድረስ ግን እነዚህ ችግሮች አሉ፡፡ ከዚህ በዘለለ ግን ስልጠና ብለን በምናስባቸው ላይ ከዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ባለሙያዎችም ይጋበዛሉ፡፡
ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ጋርም በመነጋገር ስልጠናዎች ይሰጣሉ፡፡ ግን ሰው ሰብስቦ ለማሰልጠን በሚደረግ ጥረት ፌዴሬሽኑ በራሱ ስልጠና ለመስጠት ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት አለበት፡፡ ሌላው አገር አቀፍ ደረጃ ዩኒቨርሲቲዎች ውድድሮች ሲያካሂዱ በወንድም በሴትም ይሳተፋሉ፡፡ በዚህ ስፖርት በርካታ ተመልካቾችም ይገኛሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲዎች እነዚህን ክለቦች አቅፈው ቢይዙ መምህራን ሆነ መኝታ ክፍሎች ብሎም አስፈላጊ ግብዓቶች ስላሏቸው ክለብ ቢመሰርቱ ተጠቃሚ ሆናሉ፤ በርካታ ለውጥም ያመጣሉ፡፡ ይህን ታሳቢ በማድረግ በሚቀጥለው ዓመት ለሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የክለብ ግብዣ ለማድረግ ታስቧል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የእጅ ኳስ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እንዲያድግ ጥረት ማድረግ እንደተጠበቀ ሆኖ ስፖርታዊ ጨዋነቱስ አብሮ እንዲያድግ ምን እየተሠራ ነው?
አቶ ፍትህ፡- ስፖርታዊ ጨዋነት ትልቅ ፈተና እየሆነ ነው፡፡ የስፖርት ሜዳዎችም ከስፖርዊ ስሜት ውጪ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ስለዚህ አሰልጣኞች በሰልጣኞቻቸው ላይ በሚገባ መሥራት አለባቸው፡፡ ብዙ ጊዜ የግጭት ምንጭ የሚሆኑት ተጫዋቾች ናቸው፡፡ እንደ ቀልድ ሜዳ ላይ በስሜት የሚያሳዩት ሁኔታ ብዙ ችግሮችን እያመጣና እየተቀጣጠለ ወደ ተመልካች እየገባ ነው፡፡ እንደ ፌዴሬሽን በዚህ ላይ ትኩረት ተደርጓል፡፡
ባለፈው ዓመት በተካሄደው ውድድር ላይ ችግሮች ተገምግመዋል፡፡ ከጥቃቅን ችግሮች በዘለለ የከፋ ነገር አልነበረም፡፡ ጥረቱ እንዳለ ሆኖ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ውጪ ያለን ስሜት ወደ ሜዳ ይዞ መግባት ይስተዋላል፡፡ ዳኞች ያለአግባብ ሲወስኑም ህጋዊ መንገድን መከተል ቀርቶ ነገሮችን ወደ ሌላ መንገድ መተርጎም በሁሉም ስፖርት ፈታኝ በመሆኑ ተጫዋቾች ላይ መሥራት እንደሚገባ ተግባብተናል፡፡ ከአሁኑ የተስፋ ብልጭታ እያሳየ ያለ ስፖርት በመሰል አላስፈላጊ ድርጊቶች እንዳይታወክ እየሠራን ነው፡፡ ስፖርት መመራት ያለበት በገለልተኛ ስሜት እና በፍፁም ጨዋነት ነው፡፡ ስፖርት የአንድነት መድረክ መሆኑንም ሁሉም አካል ሊገነዘብ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ እያመሰገንኩ የስፖርቱ ቤተሰብ ነገ የኢትጵያን የእጅ ኳስ ስፖርት በምን ደረጃ ይጠብቅ?
አቶ ፍትህ፡- እጅ ኳስ የተሻለ ቦታ ለመድረስ ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በዞን አምስት ‹‹ኤ›› ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በወንድም በሴትም ሻምፒዮና ሆነናል፡፡ በዚህ በጣም ስኬታማ ነበርን፡፡ ፕሪምየር ሊጉ መጀመሩ ትልቅ ነገር ሲሆን፤ አገር ወክለው የሚሳተፉ ተጫዋቾችን የማግኘት ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ይህ ጥሩ ተስፋ ነው፡፡ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን ወክለው ግብፅ ላይ ለሚካሄድ ውድድር ለመሄድ ዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ ይህ ጥሩ ተሞክሮ ለመቅሰም የሚያስችል ነው፡፡ ከኦሎምፒክ ኮሚቴ ጋር ለመሥራትም ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ በአንዴ ውጤት ባይመጣ እንኳን የተጠራቀመ ልምድ አንድ ቀን ወደ ውጤት ይቀየራል፡፡ በአስራ አንዱ ክልሎችም ቢያንስ በአንድ ትምህርት ቤት አንድ ክለብ እንዲኖር በማሰብ ከዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን ጋር ለመሥራት ታስቧል፡፡ በአጠቃላይ የእጅ ኳስ ስፖርት እንዲመነደግ ጥረት ተጀምሯል፤ ይህንንም ሁሉም አካላት ሊደግፉትና ሊያግዙት ይገባል፡፡

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

Published in ስፖርት

በአንድ የእራት ግብዣ ላይ የጽድቅና የኩነኔ ጉዳይ ተነስቶ ሞቅ ያለ ክርክር ተከፈተ፡፡ በዚህ ግብዣ ላይ ምሁራዊ አስተያየት መስጠት የሚችል ዝነኛ ሰው ቢገኝም በክርክሩ ውስጥ ሳይሳተፍ ቁጭ ብሎ ያዳምጥ ነበር፡፡ አጠገቡ የተቀመጡ አንዲት ሴት ወይዘሮ ወደ ሰውየው ዘወር አሉና ‹‹ምነው አንተ ብቻ ዝም አልክ ሀሳብህን ለማወቅ እፈልጋለሁ›› ብለው ቢጠይቁ ሰውየው እንደመ ተከዝ አለና ‹‹እሜቴ ይቅርታ ያድርጉልኝ ዝም ያልኩት ወድጄ አይደለም፡፡ በሁለቱም ቦታዎች ወዳጆች ስላሉኝ ነው›› ብሎ መለሰላቸው፡፡  
እኔም ለብዙ ጊዜያት ዝም ያስባለኝ ጾታ ነክ አስተያየት ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ለማንም እንዳላደላ ከሁለቱም ተፈጥሬአለሁና ነው፡፡ ሰሞኑን ግን እንዲሁ ከመሬት ተነስቼ ሆድ ይብሰኛል፡፡ ‹‹ያልተመረመረ ህይወት ሊኖረው አይገባውም››፤ ‹‹ሰው በልቡ እንደሚያስበው እንዲያው ነው›› የሚሉትን የጥበብ ቃላት አስብና በሬን ዘግቼ፣ ብእሬን አሹዬ ልሙጥ ወረቀት ከፊቴ ከምሬ የአእምሮዬን ጓዳ እበረብራለሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ በእፍረት የሚያሸማቅቅ፤ አንዳንዴ ደግሞ በትእቢት ልብን የሚያሳብጥ ነገር ይገጥመኛል፡፡ በተለይ የወንዶች ጉዳይ ከሴቶች ጉዳይ ጋር እኩል ቦታ ሳያገኝ ሲቀር፡፡ (የወንዶች ጉዳይ ከሚለው ፊልም ውጪ) ማለቴ ነው፡፡
ዓለም አቀፍ የሴቶች የእኩልነት ቀን (ማርች ስምንት) በመላው ዓለም ትናንት ተከብሮ ውሏል፡፡ የዓለም የሴቶች ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ እየተሻሻለ ቢመጣም የሴቶች እኩልነትም ሆነ ሴቶች በጾታቸው ሰበብ የሚደርስባቸው አድልዎ ጨርሶ አልተወገደም በሚል ሰበብ ማለት ነው፡፡ የወንዶችን ማን አየውና!
በቀኑ ባለ አስር ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል አሉ፡፡ ወደ ፊት ሰርቼ ያልፍልኛል ከማለት ይልቅ አንድ ሀብታም ወንድ አግብቼ ሀብታም እሆናለሁ የምትልን ሴት አስተሳሰብ ማስቀየር (እነ ሊሊ፣ሺሺ እና ቲቲን ለማለት ይሆን)፣ ሴቶችን በማበረታታት ሰበብ በስውር የስነ ልቦና ጥቃት የሚገድል ‹‹ሴቶች ይበረታታሉ›› የሚል የስራ ማስታወቂያን ማስቀነስ፣ የሴትን ልጅ ውበት በማድነቅ ሰበብ ወይም እላከፋለሁ ብሎ የሚሳደብ እርጥብ ወንድን አስተሳሰብ ማጥፋት፣ የሴት ልጅ አንድ ቤተሰብ ውስጥ መወለድ እንደ ገቢ ምንጭ የሚያይ ቤተሰብ (ወደ ውጭ የሚላክ ቡና አስመሰሉት እኮ) ለማንኛውም ይህንን መጥፎ ሀሳብ ድራሹን ማጥፋት፣ ቁንጅናዋን ለሁሉም የዓለም ጥያቄ መልስ አድርጋ የምታቀርብ ሴትን አመለካከት መቀልበስ፣ ሴት ልጅ ለመውለድ ብቻ ነው የተፈጠረችው ብሎ የሚያስብ ወንድን አስተሳሰብ ማስወገድ፣ እኔ ቤት ካልመጣሽ ውጤትሽ ‹‹ኤፍ›› ነው ብሎ የሚያስፈራራ እርጥብ የ‹‹ካምፓስ›› መምህር አስተሳሰብን መንጥሮ ማጥፋት፣ ሴት ልጅ አትጋብዘኝም የሚልን ወንድ ስነ ልቦና ማስለወጥ በሚሉ ግሳጼ አዘል መፈክሮች እለቱን አክብረውት ቢሆንስ የሚል ሃሳብ መጣብኝ፡፡
ለመሆኑ በዚህች ምድር ላይ በጾታ በኩል በተጠንቀቅ የሚከበረው ቀን የሴቶች ብቻ ይሁን ብሎ ፍቃድ የሰጠው ማን ይሆን? ለእኔ እንደሚገባኝ የሴቶችን ቀን ብቻ ለይቶ ማክበር ምንም እንኳን ሴቶች በማህበረሰቡ ውስጥ ያላቸው የተሳትፎ ድርሻ ከዚህ በፊት በነበረው የአመለካከት ችግር ጭቁን እንዲሆኑ ተደርጎ የነበረውን ወደ ተሻለ የእኩልነት መንፈስ እንዲያመጣ አጋዥ ቢሆንም፤  የሴቶችን ቀን ማክበር ወንዶችን ለማስቀናት መሆን የለበትም፡፡ በነገራችን ላይ እኔም ሀሳቤን የምሰጠው ቀንቼ አይደለም፡፡
የወንዶች ተጽእኖ አሁንም ጎልቶ በሚታይ ባት ዓለም ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ ሴቶች ግን ጥቂት አይደሉም፡፡ እንዲያውም የሴቶችን ያህል ተጽእኖ እየደረሰባቸው የሚገኙ በርካታ ወንዶች አሉ፡፡ በተለምዶ በኢትዮጵያ ውያን ዘንድ የሴት ስራ፤ የወንዶቸ ስራ በሚል እሳቤ ቡና የማያፈላ ወንድ- ነገር ግን ጉዱ የሚፈላ፣ ቤት የማይጠርግ - ነገር ግን ኪሱ የሚጠረግ ወንድ፣ ልብሱን የማያጥብ ነገር ግን - በላብ የሚታጠብ ወንድ፣ አሁንም ድረስ አለ፡፡ ለመሆኑ ወንድና ሴቶችን መለየትስ ይቻል ይሆን? አለባበሱ እንደሆነ ተወራራሽ ሆኗልና ነው፡፡ ታዲያ የወንዶች ቀን ተብሎ ቀን ቢሰየምና ቢከበር አያንስም ትላላችሁ?
እንደኔ እምነት ልክ እንደ ሴቶች ቀን በወንዶች ጉዳዮች ዙሪያ የሚታዩ ነገሮች መንጸባረቅ አለባቸው፡፡ በዓለም ደረጃ ለጾታ እኩልነት የሚሰሩ ወንዶች እውቅና ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ኧረ እንዲያውም የወንድ ልጅን ጥቃት ለመከላከልና ለማስወገድ የሴቶች አጋርነት ወሳኝ ነው ቢባልስ? እኔን ያስማማኛል፡፡
በዚህ ዘመን ሴት መሆን እድለኝነት ነው፡፡ ሴት የመሆን ጉዳቶች ላይ ተደጋጋሚ ነገር ሲነገር ሰምተናል፡፡ የቤት ውስጥ የስራ ጫናው፣ ማህበራዊ ኃላፊነቱ፣ የዘመን አመጣሽ ተግዳሮቶቹ፣ ከወንድ ይልቅ ለባህልና ለማህበረሰብ ኃላፊነት በሴቶች ላይ መጫኑ፣ የሚታየው አካላዊ ጉዳት ወዘተ... ለማስቀረት የተለየ ድጋፍ እየተደረገ ነው፡፡ ለወንዶችስ?
መሪነትስ ቢሆን አመራሩ እኮ የሴቶች ነው፡፡ በአደባባይ ወንዶች ወንበር ላይ ይቀመጡ እንጂ የወንዶችን የውጭ የታይታ ዓለም ከውስጥ ሴቶች ይቃኙታል፡፡ ቢበዛ መንገዱን ማወቅ ይጠይቅ ይሆናል እንጂ የሚፈለገውን አቅጣጫ የማስያዝ የተደበቀ ስልጣን የሴቶች መሆኑን አንርሳ፡፡ ጠይቆ እምቢ አለመባል፣ የውበትና የኃላፊነት እመቤት መሆን፣ ማህበረሰብን መገንባት እና ህይወትን ማጣፈጥ የሴቶች መታደሎች ናቸው፡፡ በትናንትናው እለት የታተመው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንኳን በልዩ እትሙ ሲወጣ በጋዜጣው ላይ የተሳተፉት ሙሉ በሙሉ ሴቶች መሆናቸው ሴቶች ከወንዶች አኩልና ከዚያም በላይ መስራት ስለመቻላቸው ምስክር ነው፡፡ ወንዶችም የሴቶችን ያህል ማህበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት ትልቅ የሞራል ስንቅ እንዲያገኙ መደገፍ አለባቸው ባይ ነኝ፡፡
ወንዶች በፍቅር መውደቃቸውን የሚያሳዩ ምልክቶች ተብሎ ማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ከመለጠፍ ይልቅ መች ቀን ተሰይሞልን ተከብሮ ያውቃል? ወንዶች የህብረተሰቡ ግማሽ አካል ናቸው፤ ወንዶችን ማስተማር ህብረተሰቡን ማስተማር ነው፤ የወንዶች ጥቃት ይብቃ፤ የሚሉ መፈክሮች ለወንዶችም ቢውሉ ምናለበት? ዋናው ነገር ቀና ማሰብ ነው፡፡
ይህ ነገር አጽንኦት ተሰጥቶት ተግባራዊ እንዲደረግ ህልም ማየቴ አይቀርም፡፡ ያው ከድል በዓላቶቻችን ውጪ ያሉትን ቀናትና ስያሜአቸውን ያስለመዱን ባህር ማዶ የሚገኙ አገራት ስለሆኑ ለሴቶች የወጣላቸው ቀን ለወንዶችም ይወጣና ይከበርም ዘንድ ህልም ባልም ይሻላል ብዬ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ሲኒማ ቤቶች ረጅም ጊዜ ከቆየውና በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን ካተረፈው ‹‹የወንዶች ጉዳይ›› ፊልም በስተቀር ወንዶች ላይ ያተኮረ ትልቅ አገራዊ አጀንዳ ሲነሳ አላየሁም፡፡ ይልቁንም ወንዶች ለብዙ የማህበራዊ ሂስ ተጋላጭ ሆነዋል፡፡ አንዷ ወዳጄም ይህንኑ አስመልክታ ስታጫውተኝ ‹‹ወንዶች በቆንጆ ሴቶች የሚቀርቡ የቴሌቪዥን ዜናዎችን ማስታወስ አይችሉም›› አለችኝ፡፡ (የት እየሄዱ ይሆን?) ይህም የሆነበት ምክንያት እንዲህ አይነት መስብህነት ያላት ሴት ፖለቲካ፣ ስፖርታዊና ጦርነት ነክ ጉዳዮች መያያዝ አለባት ብለው ስለማያስቡ ነው፡፡ ብላ አብራራችልኝ፡፡ እውነትና ሀሰቱን ግን ለተመልካች ብንሰጠው ይሻላል አልኳት በሆዴ፡፡  ይሁን እንጂ ተመሳሳዩ ትውስታ ጥንካሬና ድክመት በሴት ቴሌቪዥን ተመልካቾች ላይ አልታየም፡፡
የሴቶች ቀን መከበሩ ስለ ሴቶች እንዲወራ እንደሚፈለገው ሁሉ፤ የወንዶች ቀን ተከብሮ ስለ ወንዶች እንዲወራም የሚሻው የወንድ ቁጥር ብዙ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ቀን ታሳቢ ተደርጎ ይዋል እንጂ የስራ ዝግ ቀን አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ቀኑን ሳይሆን እስኪ መጀመሪያ ሴቶችን እናክብር የሚል ምክር ቢጤም አለችኝ፡፡ ሴቶች በሰላም ሲኖሩ ነው ቀናቸውን የምናከብረውና፡፡ ‹‹ማርች ስምንት›› የሴቶች ቀን ተደርጎ ሲከበር ሌሎቹ ቀናት የወንዶች ቀናት እንዳልሆኑም ይታሰብበት፡፡

አዲሱ ገረመው

Published in መዝናኛ

ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር በሚደረገው ጥረት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት መስፋፋት አይነተኛ ሚና አለው፡፡ በተለይ ህጻናት ሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርትን ከመጀመሪያ ትምህርት ቤት ጀምሮ በተግባር እንዲያውቁት ለማድረግ ትኩረት በመስጠት መስራት የቴክኖሎጂ ሽግግሩን ከማፋጠኑ ባሻገር አዳዲስ ዲዛይኖችንና ፈጠራዎች በአገር ውስጥ እንዲያድጉ ይረዳል፡፡ ከአገሪቱ ዕድገትና ለቴክኖሎጂ ካለን የቅርበት ደረጃ አኳያ ተማሪዎች የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርትን መማር የሚጀምሩት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲደርሱ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በንድፈ ሃሳብ እንጂ በተግባር ሳያውቁትና ሳይለማመዱት ኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርትን የሚማሩ እንዳሉ እሙን ነው፡፡ በዚህ ረገድ አይከን ኢትዮጵያ የሮቦቲክስ ስልጠና እና ውድድር ማዕከል ከታች ክፍል ያሉ ተማሪዎች የሳይንስ፣ የሂሳብ፣ የቴክኖሎጂና የኢንጂነሪንግ እውቀታቸው እንዲያግድ ታዳጊዎችን ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለጎን እያሰለጠነ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡ ሳይንስና ቴክኖሎጂውን ከልጅነት ጀምሮ በተግባር እንዲለማመዱ ማድረግ ዘርፉን በቀላሉ ለመረዳት ከማስቻሉ ባሻገር ፈጠራዎች እንዲበራከቱ ያደርጋል፡፡
ልጆችን ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለጎን በተግባር የኮምፒውተር ሳይንስን እንዲረዱ፣ ፕሮግራም ማድረግ እንዲችሉና የፈጠራ ክህሎታቸው እንዲያድግ የሚያደርጉ ማዕከላት መጠናከር እንዳለባቸው ተማሪዎቹ ይገልጻሉ፡፡
በአይከን ኢትዮጵያ የቬክስ ሮቦቲክ ስልጠና እየወሰደ ያለውና የእንግሊዝ ዞን 9ኛ ክፍል ተማሪ ነብዩ ዳንኤል ‹‹እኛ ሀገር ተማሪዎች ኮምፒውተርን ማወቅ የምንጀምረው ሁለተኛ ደረጃ ስንደርስ ነው፡፡ ለዚያውም የምንማራቸው ቀላል የኮምፒውተር ክፍሎችን ማለትም ማይክሮ ሶፍት ወርድና ኤክስኤል የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆነን እንኳ ከውጨኛው (ሃርድ ዌር) ክፍሉ ውጭ ሌላ የምናውቅበትና የምንመረምርበት ሁኔታ የለም፡፡ በአደጉ አገራት ግን ኮምፒውተርን ከልጅነታቸው ጀምሮ ውስጣዊና ውጫዊ ክፍሉን በተግባር እየተማሩት ስለሚያድጉ ከተማሪነት ሳይወጡ የፈጠራ ባለቤት ይሆናሉ፡፡›› በማለት ይናገራል፡፡
ተማሪ ነብዩ እንደሚለው፤ አይከን ኢትዮጵያን ከተቀላቀልኩ በኋላ በቬክስ ሮቦቲክስ አማካኝነት የኢንጂነሪንግ፣ ፕሮግራሚንግና ዲዛይን ስራዎችን ማወቅ ችያለሁ፡፡ ይህም ማለት ሮቦቶች እንዴት ዲዛይን እንደሚደረጉ፣ እንዴት ፕሮግራም ማድረግና ማንቀሳቀስ እንደሚቻል ኢንጂነሪንጉን ጭምር ያስተምራል፡፡ ሮቦቶችን ፕሮግራም በማድረግና በመገንባት እንደ ሰዎች ማዘዝና ስራ ማሰራት እንደሚቻልና ለዚች አለም ምን ያህል ጠቃሚ መሆናቸውን ያስተምራል፡፡ በተግባር ልምምድ ውስጥ ዲዛይን፣ ፕሮግራሚንግና ኢንጂነሪንግ አብረው ይሰራሉ፡፡ ይህም የሳይንስና የቴክኖሎጂ እውቀትን ለማሳደግ፣ አዳዲስ ዲዛይኖችን ለመፍጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡
በሮቦቲክስ ስልጠናው ኤሌክትሪካልና ኢንጂነሪንግን ጨምሮ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የሚሰጡ አይ.ሲ.ቲ፣ ዲዛይንና ፕሮግራሚንግ እንዲሁም ‹‹ጃቫ፣ ሲ. ፕላስ. ፕላስ›› የመሳሰሉ ውስብስብ የኮምፒውተር ትምህርቶችን በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መማር መቻሉ ወደፊት በዘርፉ ውጤታማ ለመሆን ይረዳል፡፡ በመሆኑም መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ቢሰጥ ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር አስተዋፅኦው ከፍተኛ ነው በማለት ተማሪ ነብዩ ይናገራል፡፡
ለሳይንስና ሒሳብ ትምህርቶች ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለውና ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን የሚገልጸው ተማሪ ነብዩ፤ አንድ አገር ከፍተኛ ቴክኖሎጂ እድገት ላይ ለመድረስ በሂሳብና በሳይንስ ትምህርት ዘርፎች በቂና የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ በተግባር የተደገፈ ስልጠና መሆኑ ደግሞ ሳይንሱን በቀላሉ ለመያዝና ለአዲስ ፈጠራ በር ይከፍታል በማለት ይገልጻል፡፡
በአንዱዴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዘጠንኛ ክፍል ተማሪ የሆነችውና በቴሌቪዥን በተመለከተችው የአይከን ኢትዮጵያ ማስታወቂያ ወደ ማዕከሉ መምጣቷን የምትገልጸው ሀናን ቢላል፤ የሮቦት ሳይንስን መማሯ ሮቦቶችን ዲዛይንና ፕሮግራም ከማድረግ ባሻገር ቡድናዊ አሰራር እንድትለምድ፣ የኮምቲውተር ክህሎታችን እንዲያድግ፣ በቡድኑ የሚመጡ የተለያዩ ሃሳቦችን በማቀናጀት ስራን ማቀላጠፍን መማሯን ትገልጻለች፡፡
የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ እንደመሆኔ መጀመሪያ ወደ ማዕከሉ መጥቼ ሳይንሱን ለመረዳት ስሞክር ውስብስብ እንደመሆኑ ግር ይላል፡፡ ሆኖም ትኩረት ተሰጥቶ መከታተል ከተቻለ ሁሉም ነገር ቀላል መሆኑንና አይቻልም የሚል መንፈስ መኖር እንደሌለበትም ያስተምራል የምትለው ተማሪ ሀናን፤ ዲዛይኒንግን በተገቢው ሁኔታ በመማር ‹‹አርክቴክት›› መሆን እንደምትፈልግ ታብራራለች፡፡ የሮቦቲክስ ስልጠናው መጀመሪያ በኪት የሚሰሩ ስራዎችን ስለሚያስተምር ይህም ፊዚክስ ላይ ቀላል መኪናዎችን (ዊል እና አክስል እንዲሁም) በከራ፣ ፑሊዎች፣ ኢፈርት፣ ሎድ፣ ፈርክለም/ የመሳሰሉት የፊዚክስ ጽንስ ሃሳቦች እንዴት እንደሚሰሩ በቀላሉ ስለሚያስተምር ፊዚክስ ትምህርት ላይ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል በማለተ ገልፃለች፡፡
ተማሪ ሀናን አይከንን መቀላቀሏ በጽንሰ ሀሳብ የምታውቀውን በተግባር እንድትሠራ እንደረዳት፣ በጥቂት ወራት ውስጥ የተለያዩ ሮቦቶችንና ማሽኖችን መሥራት መቻሏን፤ እንደ ወኪንግ ሮቦት፣ ሄሊኮፕተር፣ ሮቦቲክ አርምና ሌሎችም ዓይነት ሮቦቶች ለመስራት እየሞከረች መሆኗን ትናገራለች፡፡
  የአይከን ኢትዮጵያ መሥራችና ዳይሬክተር አቶ ሰናይ መኰንን፤ በአሁኑ ወቅት በርካታ አገሮች ተማሪዎችን በጽንሰ ሐሳብ ከማስተማር ይልቅ ትኩረት ያደረጉት ተግባር ላይ ነው፡፡ ይህም ተማሪዎቹን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ይረዳል፡፡ በተለይ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ እውቀት ያላቸውን በብዛት ከማፍራት ይልቅ በተግባር የተደገፈ ስልጠና ያገኙ ቴክኒሽያኖችን ማፍራት ተገቢ በመሆኑ ድርጅቱ ትኩረት ያደረገው በተግባር ላይ ነው፡፡ በአገሪቱም ይህን ማጠናከር ከተቻለ ለኢኮኖሚያዊ ሽግግሩ እገዛ ይኖረዋል፡፡ በተለይም እስካሁን ባለው ሁኔታ በ20 እና በ30 እድሜያችን ያገኘነውን የቴክኖሎጂ ዕውቀት ህጻናት በ10 እና በ15 እድሜያቸው ቢያገኙት ትውልዱ በቀጣይ የተሻለ ነገር የመስራት አቅም ይኖረዋል፡፡ ተማሪዎች ጽንሰ ሀሳቡን በተግባር እንዲማሩ ማድረግ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ በሌሎች አለም ያለው ተሞክሮም ይህ ነው ይላሉ፡፡
ትምህርት ቤቱ ከተቋቋመ ወደ ሰባት ዓመታት ተቆጥሯል፡፡ ትምህርቱን የሚሰጠውም እንደ ደጋፊ ትምህርት ቅዳሜና እሑድ ሲሆን፤ ከተማ አቀፍ የጥያቄና መልስ ውድድር ከተዘጋጀ በኋላ ተማሪዎቹ በሒሳብና በሳይንስ ትምህርቶች ላይ ያላቸው ችሎታ ተገምግሞ በውጭ አገር ከሚገኙ ተማሪዎች ጋር በአህጉር ደረጃ እንዲወዳደሩ አድርጓል፡፡ የአሜሪካ ብሔራዊ የጠፈር ማዕከል የነገዎቹን ጠፈርተኞች ከመፍጠርና ሳይንሱንም ከማስፋፋት አንፃር በየዓመቱ ከተለያዩ የዓለም አገራት የተውጣጡ ታዳጊ ተማሪዎችን ለጉብኝት ይጋብዛል፡፡ በዚህ ለመሳተፍ በተደረገው ጥረት ዓመታዊ ውድድሮች ላይ አሸናፊ ለሆኑትና በመጨረሻው ዙር በሕንድ የተካሄደውን ዓለም አቀፍ ውድድር አሸንፈው ለተገኙ ተማሪዎች ዓለም አቀፉን የጠፈር ምርምር ተቋም እንዲጐበኙ ተደርጓል ያሉት አቶ ሰናይ፤ ይህን አጠናክሮ ለመቀጠል ጥረት እየተደረገ ነው ይላሉ፡፡
አቶ ሰናይ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ስር የተቋቋመ ባዮቴክኖሎጂ፣ ከፌዴራል ሂሳብና ሳይንስ ማስፋፊያና ማሻሻያ ማዕከላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው፤ ተማሪዎቹ በሳይንስ፣ በኢንጂነሪንግና በፕሮግራሚንግ ክህሎታቸውን በማሳደግ በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ ጥሩ ውጤት በማምጣት የተሻለ እድል የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት እየሰራ መሆኑን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ የቬክስ ሮቦቲክስ ዲዛይንና ፕሮግራሚንግ ተማሪዎች ትልቅ አቅም ያላቸው ግዙፍ የሆኑ ሮቦቶችን በተለያየ መልኩ በመስራት ማቅረብ ስለሚችሉ በአዓለም አቀፍ መድረክ የሚደረገው ውድድር የማዕከሉ ተማሪዎች የተሻለ ስራ እንዲሰሩ እንደሚያስችላቸው አስረድተዋል፡፡
  የፈጠራ ክህሎቶችን ለማሳገድ አዳዲስ ዲዛይኖችን ለመስራት መሞከር ያስፈልጋል፡፡ ተማሪዎች እየሰሩ መማር አለባቸው፡፡ የኢንጂነሪንጉ ዘርፍ ሊያድግ የሚችለውም እየሰሩ፤ ሲበላሽ እያስተካከሉ ሲማሩትና አዲስ ነገር ለመፍጠር በተግባር ጥረት ሲደረግ ነው፡፡ ለአብነት ባለፈው በአገሪቱ አውሮፕላን ሰራ የተባለው ወጣት ኢንጂነሪንጉን በተግባር እየሰራ መማር መቻሉን ተረድቻለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ አዲስ ነገር ወደ መፍጠር ወይም የተለየ ዲዛይን ወደ መስራት ያመራል፡፡ ኢንጂነሪንጉ በተግባር ሲደገፍ የተለየ ነገር ለማምጣት ይረዳል፣ የፈጠራ ስራም ያድጋል በማለት አቶ ሰናይ ያብራራሉ፡፡
  እንደ አቶ ሰናይ ገለጻ፤ በአሜሪካን አገር በየአመቱ በሚካሄደው የቬክስ ሮቦቲክ ውድድር እስከ 22ሺ የተለያዩ አገር ተማሪዎች የሚወዳደሩ ሲሆን፤ ዘንድሮ ሚያዚያ ወር ላይ በአሜሪካን አገር በሚካሄደው ዓለም አቀፍ ውድድር ተማሪዎች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ በውድድሩ ለማሸነፍም ሮቦቶችን በተለያየ ዲዛይን በመስራት ልምምድ እያደረጉ ነው፡፡ በውድድሩም እስከ 40 የሚደርሱ ተማሪዎችን ይዞ ለመሄድ ታስቧል፡፡ ቬክስ ሮቦቲክስ ስልጠናው ልጆች ችግሮችን በተለያየ መንገድ የመፍታትና አንድን ነገር በጋራ የመስራት ባህል እንዲያጎለብቱ ይረዳል፡፡ ባለፉት ጊዜያት በካናዳ 16 አገሮች በተካፈሉበት ውድድር የአይከን ኢትዮጵያ ተማሪዎች የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘት ችለዋል፡፡ ቻይና በነበረው ውድድር ከአፍሪካ ኢትዮጵያ ብቻ የነበረች ሲሆን፤ በውድድሩ በቡድን በመስራት ባሳዩት ብቃት የቤዝቲም ሽልማት አግኝተዋል፡፡ የዋንጫ ሽልማትና ልዩ ልዩ ሜዳሊያዎች በየዘርፉ ማግኘት ችለዋል፡፡ ይህም ልጆቹ ሮቦቶቹን በአዲስ ዲዛይን መስራት እንደቻሉና የሰሩት ዲዛይንም እውቅና ማግኘቱን አረጋግጧል፡፡
ማዕከሉ በሳይንስና ሂሳብ ብቃት ፍላጐት እያላቸው በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ተሳታፊ መሆን ያልቻሉ ተማሪዎችን  በነጻ እንዲማሩ ድጋፍ እያደረገ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በወርክሾፑ ቅዳሜና እሁድ የሚማሩ 132 ተማሪዎች መኖራቸውን አቶ ሰናይ አስረድተዋል፡፡
በቦሌ መሰናዶ ትምህርት ቤት የኮምፒውተር ሳይንስ መምህርና በአይከን ኢትዮጵያም መምህር የሆነው ቀጀላ ዋቅቶላ እንደሚናገረው፤ ‹‹እስካሁን ባለው ሁኔታ በአገሪቱ ፕሮግራሚንግ የሚባለውን የምንማረው በዩኒቨርሲቲና ኮሌጅ ደረጃ ብቻ ነው፡፡ ይህም ተማሪዎች ዘርፉን ለተወሰነ ጊዜ ብቻ እንዲያጠኑት ስለሚያደርግና በተግባርም በተደገፈ መልኩ በተደጋጋሚ ስለማይማሩት የተሻለ የፈጠራ ስራ እንዳይሰሩ አድርጓል፡፡ እንደ አይከን ኢትዮጵያ ያሉ ማዕከላት ቢበራከቱ ልጆች ፕሮግራሚንግና ዲዛይንን ከልጅነታቸው ጀምሮ እንዲማሩ ስለሚያደርግ በቀላሉ ዘርፉን እንዳያውቁት አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን ለመስራት እንዲሁም የቴክኖሎጂ ምጥቀት ለማምጣት ያግዛቸዋል፡፡›› ነው የሚለው፡፡
በመንግስት ትምህርት ቤቶች የአይ.ሲ.ቲ ግብዓቶችን በማሟላት ተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ትምህርት እንዲያገኙ ከማድረግ አኳያ ሰፊ ክፍተት አለ፡፡ ይህን ለማስተካከል ከንድፈ ሃሳብ (ቲዎሪ) ትምህርት ይልቅ ለተግባር ትምህርት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡ በተለይም በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ተሞክሮው ተግባራዊ ቢደረግ የተሻለ ውጤት ለማምጣትና የልጆቹን አዕምሮ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ለማሳደግ ይረዳል፡፡ ይህም አገሪቱ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የምታደርገውን ጥረት ያፋጥናል በማለት መምህር ቀጀላ ይናገራል፡፡

ዑመር እንድሪስ

Published in ማህበራዊ

ማንም ሰው በሀገሩ ማንነቱንና ባህሉን ጠብቆ ቢኖር ደስተኛ ነው፡፡ ሆኖም ህይወት ውጣ ውረድ ላይ የተመሰረተች የማታቋርጥ ጉዞ ነችና ሰዎች በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ሀገራቸውን ጥለው ለመሰደድ ይገደዳሉ፡፡ በተለይ የዘመናዊ የመገናኛ አውታሮችና የቴክኖሎጂ መስፋፋት የሰዎችን የመዘዋወር ፍላጎት ከዕለት ወደ እለት እየጨመረ እንዲመጣ አድርጓል፡፡
ህጋዊ ስደት የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ከማስገባት ጀምሮ የሥራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ፣ የቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት ለማዳበር እንዲሁም የተሻለ የትምህርት ዕድል ለማግኘት መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ ሆኖም ሰዎች መደበኛ ባልሆነ በሕገወጥ መንገድ የሚያደርጉት ጉዞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን  መረጃዎች   ያመለክታሉ፡፡ በሕገወጥ መንገድ የሚያደርጉት ጉዞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በሕገወጥ መንገድ የሚደረገው ስደት ከላኪ፣ ከተቀባይ እና ከመሸጋገሪያ (ትራንዚት) አገሮች አካሔድ ቁጥጥር ውጭ የሚደረግ በመሆኑ ተዘዋዋሪዎቹ ለማንኛውም አደጋ ተጋላጭ ናቸው፤ ከለላ የሚያገኙበት የህግ አግባብም የለም፡፡
ጉዞዎቹ በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ግለሰቦች ስለሚወሰኑ እንደ ሁኔታዎች አመችነት ከመደበኛ ትራንስፖርት ጀምሮ በሌሊት፣ ቀን በበረሃ ፣ በባሕር እና በውቅያኖስ ማጓጓዝን፣ ኬላዎችን እና የቁጥጥር ቦታዎችን ተሰውሮ ማለፍን ያካትታል፡፡ ይህም ስደቱን አስከፊና በሞት ቀጣና ላይ ተረማምዶ የማለፍ ያህል ያከብደዋል፡፡ ተጓዦቹ ላይ ወሲባዊ ጥቃት፣ የዝሙት አዳሪነት፣ ባርነትና መሰል ተግባር ከፍ ሲል ጠቃሚ የሰውነት አካል ክፍላቸውን አውጥቶ እስከ መውሰድ ያደርሳል፡፡
በዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት የብሔራዊ ፕሮግራም ባለሙያ ወይዘሮ ልዩነት ደምስ እንደሚሉት፤ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ዓለም አቀፍ ችግር ከመሆኑ ባሻገር በሰዎች ላይ የሚፈጸም ዘመናዊ ባርነት እየሆነ መጥቷል፡፡ ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ማህበራዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫናው እየበረታ ነው፡፡ ይህ ችግር በአገሪቱም በስፋት በመንሰራፋቱ ወጣቱ ባልተጨበጠ ተስፋ በህገወጥ አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ለሕገወጥ ስደት ሲዳረግ ይታያል፡፡
ከአገሪቱ በርካታ ዜጎች ወደ መካከለኛው ምስራቅ በህገወጥ መንገድ ቢሰደዱም ከ780ሺ በላይ ስደተኞች ከጎረቤት ሀገሮች ኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳንና ሶማሌላንድ ወደተለያዩ ሀገሮች ለመሸጋገር በአገሪቱ በተለያዩ ክፍሎች ተጠልለው ይገኛሉ ያሉት ወይዘሮ ልዩነት፤ በአሁኑ ወቅት ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በህብረተሰቡ፣ በመንግሥትና በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ሰፊ ትኩረት በማግኘቱ በሀገር ደረጃ መንግሥት ብሔራዊ ግብረ-ኃይል አቋቁሞ በመስራቱ ከዓመት በፊት ከነበረው የተወሰነ መሻሻል ያሳያል ብለዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ኬንያንና ታንዛኒያን እንደ መሸጋገሪያ በመጠቀም ደቡብ አፍሪካ ለመግባት የሚጓዙ ናቸው፡፡ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል እ.ኤ.አ. በ 2016 በህገ ወጥ መንገድ ከአገር የወጡት ስደተኞች ቁጥር 20 ሺ የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ቁጥሩ ወደ 13 ሺ ዝቅ ብሏል፡፡
ሳዑዲ አረቢያ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎች እንዲወጡ ማወጇና በደቡብ አፍሪካ በስደተኞች ላይ የሚፈጸሙ ግፍና ወንጀሎች እየተበራከቱ መምጣት እንዲሁም ህገወጥ አዘዋዋሪዎች የሚያስከፍሉት ገንዘብ እየጨመረ መምጣት ዜጎች በተወሰነ ደረጃ ስደትን እንዲጠሉ በማድረጉ የወጣቶች መሰደድ እንዲቀንስ አድርጓል፤ ሆኖም ችግሩን ከመሰረቱ ለማስቀረት ብዙ መስራት ይጠይቃል ሲሉ ወይዘሮ ልዩነት ያብራራሉ፡፡
   እንደ ወይዘሮ ልዩነት ማብራሪያ፤ በገጠር አካባቢ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ስለ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ያላቸው ግንዛቤ እየጨመረ በመምጣቱ ልጆቻቸውን በማስተማር ሰፊውን ድርሻ እየተወጡ ናቸው፡፡ በችግሩ ላይ ከሚታየው ሰቆቃ ጋር ተያይዞ የተለያዩ የማህበረሰብ መሪዎችን በየአካባቢው በማጠናከርና ድርጊቱን እንዲከላከሉ በማድረግ አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡  
 ህገወጥ አዘዋዋሪዎችን ከማጋለጥ አንጻር ባለፉት ሦስት ዓመታት በአምስት ክልሎች ማለትም በአማራ፣ በኦሮሚያ በትግራይ፣ በደቡብና በሶማሌ የማህበረሰብ አወያይ ተወካይ ሰዎች ሰፊ ሥራ ሰርተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ደላሎች በማህበረሰቡ ዘንድ ለህብረተሰቡ የሚጠቅሙና የሥራ ዕድል የሚያመቻቹ ተደርገው ይታዩ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ላይ ሰፊ የሆነ የአመለካከት ለውጥ ህብረተሰቡ ዘንድ አለ፡፡ ደላሎችን ከመሸሸግ ይልቅ አጋልጠው ለህግ አካላት የሚሰጡበትና የሚያስተምሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ለመከላከልና ወጣቶቹ ተገቢ ባልሆነ መንገድ እየጠፋ ያለ ህይወታቸውን ለመታደግ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተለይ የሃይማኖት አባቶችና የትምህርት ተቋማት ከግብረ ኃይሉ ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ወይዘሮ ልዩነት አስረድ ተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የሰላም መምሪያ አስተባባሪ አቶ አዳነ ደቻሳ፤ ዜጎች በህጋዊ መንገድ ቢሰደዱ ደህንነታቸውና መብታቸው ተጠብቆ ለራሳቸውም ለሀገር ኢኮኖሚም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ካለማወቅና በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ደላሎች በመደለል በስቃይና እንግልት ወደተሞላ ህይወት ሲገቡ ይስተዋላል፡፡ ይህን መከላከል የሚችሉት ራሳቸው ስደተኞች ወይም ለመሰደድ የሚያስቡ ዜጎች እየደረሰ ያለውን በደልና ግፍ በመረዳት ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ለደላሎች ከፍለው የሚሄዱበትን ገንዘብ ሥራ ላይ ቢያውሉት በሀገራቸው ላይ የማይለወ ጡበት አጋጣሚ አይኖርም ባይ ናቸው፡፡
 ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመቆጣጠር በርካታ ተግዳሮቶች አሉ፡፡ በተለይ በድሃ ሀገሮች ከሚስተዋሉ የሥራ አጥነትና የኢኮኖሚ ችግር አኳያ ለህገወጥ ስደት የሚዳረገው ዜጋ ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት በርካታ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት ከቻሉ እልባት የማያገኝበት ምክንያት አይኖርም የሚሉት አቶ አዳነ፤ በጉዳዩ ላይ ቤተሰብ፣ የትምህርት ተቋማትና የሃይማኖት አባቶች ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለ ባቸውና ዜጎች ሀገራቸውን እንዲወድዱ እንዲሁም በሀገር ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ማስተማር እንደሚጠበቅባቸው ይናገራሉ፡፡ በትምህርትና በሥራ ምክንያት መጓዝ አስፈላጊ ከሆነ ህጋዊ መንገድ በተከተለና ለአደጋ በማያጋልጥ መልኩ መሆን አለበት ይላሉ፡፡
   የዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት መረጃ፤ በህገወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመግባት የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በ2012 እ.አ.አ 84 ሺ 376፣ በ2013 እ.አ.አ 54 ሺ 213፣ 2014 እ.አ.አ 71 ሺ 907፣ 2015 እ.አ.አ 82 ሺ 268፣ በ2016 እ.አ.አ 97 ሺ መሆኑን ያመለክታል፡፡ በተጨማሪም 2017  እ.አ.አ 8ሺ 688 ከአፍሪካ ቀንድ በሊቢያና ግብጽ በኩል በማድረግ ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው አውሮፓ ገብተዋል፡፡ 


ዜና ሐተታ
ዑመር እንድሪስ

Published in የሀገር ውስጥ
Friday, 09 March 2018 17:18

ጽናት ያቀናው ፕሮጀክት

በላብ የወረዛ ግንባሬን ለማቀዝቀዝ የእጄን መዳፍ ለአርማታ ማቡኪያ ውሃ ከሚወርደበት ሰፊ የብረት ቱቦ አፍ ላይ ዘረጋሁ፡፡ በሰፊው ቱቦ የሚንፎለፎለው ውሃ መዳፌን ሲነካኝ እሳት የጨበጥኩ ያህል ተሰማኝ፡፡ እንኳን የጋለ ግንባሬን ላቀዘቅዝ ቀርቶ የተጠበሰ መዳፌን የማቀዘቅዝበት ነገር አጥቼ ሳማትር በብረት ላይ ቆመው ብረትን የሚያነድዱ ማለትም የሚበይዱ ወጣቶችን ተመለከትኩ፡፡
እኔን የፈጀኝ ውሃ ነው! ወጣቶቹ ግን በብረት ላይ ቆመው እሳት እያነደዱ፣ እሳት እየነደደባቸው ሥራቸውን ሲከውኑ ይስተዋላሉ፡፡ ለእነርሱ ትልቁ ቁም ነገር ከላይ የምትነድደው ፀሐይ አይደለችም፣ የፈላው ውሃ የሚፈጥረው እንፋሎትም አይደለም፤ ቁምነገራቸው ሥራቸውን ትኩረት ሰጥተው መስራት ብቻ ነው፡፡ በአዕምሮዬ «የወጣቶቹ ጽናት ከየት መጣ?» የሚል ጥያቄ ተመላለስ፡፡ ጀግና ባለታሪክ ለመሆን ካልሆነ በስተቀር ገንዘብ ለማግኘት ነው ብሎ ማሰብ እጅጉን ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም ገንዘብ ለማግኘት በእሳት መፈተን ላይጠበቅ ይችላል፡፡ ወጣቶቹ ግን በእሳት ተፈትነው እየሰሩ ነው፡፡
ከሥራው ክብደትና ከወጣቶቹ ፍጥነት ጋር ብዙ ነገሮች ታወሱኝ «የህዝብ አደራ፣ አገራዊ ስሜት፣ ትልቅ ለመሆን የሚደረግ ትግል»  እውነታው ወጣቶቹ እየሰሩት ያለው ሥራ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች ከልሂቅ እስከ ደቂቅ በዕውቀታቸውና በጉልበታቸው ያለ አንዳች እረፍት ለመገንባት የሚረባረቡበትን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እውን ለማድረግ የህዝብ አደራን ይዘው ነው፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ለመጀመሪያ ጊዜ የማየት እድል ያጋጠመኝ በ2007ዓ.ም ቢሆንም ከሦስት ዓመት በኋላ ከአባይ ግርጌ ሆኜ ሽቅብ ስመለከተው «እንዳጋመስነው እንጨርሰዋለን!» የሚለው መፈክር በተግባር እውን እየሆነ መምጣቱን አረጋግጫለሁ፡፡ ዋና ግድቡ ለመጠናቀቅ እየተቃረበ ከመሆኑ ባሻገር የኮርቻ ግድብና (ሳድል ዳም) ሌሎች ማስተንፈሻዎች ከጠበቁት በላይ ተጠናቅቀው ማየት መቻሌ ደስታን ፈጥሮብኛል፡፡ ይህም ጽናት የማያሸንፈው ነገር አለመኖሩን በተግባር አረጋግጦልኛል፡፡
«በሥራ መሀል መንገራገጭ ቢኖርም ሁሉም አላፊ ናቸው፡፡ ጽናት ካለ ካሰብነው ቦታ መድረስ እንችላለን፤ የምንሰራውንና የምንደርስበትን እናውቃለን፡፡ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ግድቡ እውን ሆኖ በአደራ ለሰጠን የኢትዮጵያ ህዝብ የምናስረክብበት ቀን ሩቅ አይደለም፤ በቅርብ እውን ይሆናል» በማለት የሚናገሩት ደግሞ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ናቸው፡፡ ኢንጂነሩ ይህን ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሰሞኑን ለአገር ውስጥ የሚዲያ አካላት ግድቡ የሚገኝበትን ነባራዊ ሁኔታ ባስጎበኘበት ወቅት ነው፡፡በጉብኝቱ ተሳታፊ የነበረውና በማህበራዊ ሚዲያ የአንድ ገጽ አዘጋጅ ወጣት በረከት ስዩም «ግድቡን ስመለከት የተዘበራረቁ ስሜቶች ተሰምተውኛል፡፡ ከመጋመስ አልፎ ወደ መጠናቀቅ መድረሱ ሲያስደስተኝ ያለውን ከባድ ሙቀት ተቋቁመው የሚሰሩ ወጣቶችን ስመለከት ደግሞ ደስታዬ ተዘበራርቋል፡፡ ሙቀቱ ከባድ ነው፡፡ ሥራው ከሙያ ባሻገር አገራዊ ስሜት ይጠይቃል፡፡ ይህ በሁሉም ሠራተኞች ባይኖር ሥራው እዚህ ደረጃ ይደርሳል ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡» ይላል፡፡
ወጣት በረከት ሲናገር« በተለያየ ጊዜ በማህበራዊ ሚዲያዎች የግድቡን ግንባታ በተመለከተ ግድቡ ቆሟል የሚሉና የተሳሳቱ መረጃዎች ሲራገቡ ነበር፡፡ ከቦታው ሆኜ ስመለከተው ግን እየተጠናቀቀ መሆኑን መረዳት ችያለሁ፡፡ በተለይም በግድቡ ላይ እየተሰሩ የሚገኙ የኤሌክትሮና ሃይድሮ መካኒካል፣ የኃይድሮሊክ ስቲል ስትራክቸር፣ የትራንስሚሽን ግንባታና መቆጣጠሪያ መሳሪያዎች ተከላ አፈጻጸም ከጠበቅኩት በላይ ነው፡፡ ይህም በማህበራዊ ሚዲያ ይነዙ የነበሩ ወሬዎች በተጨባጭ ስህተት መሆናቸውን እንዳረጋግጥ አስችሎኛል፤ ግድቡ በዚህ ደረጃ መጠናቀቁን ህዝብ ሙሉ በሙሉ ያውቃል ለማለት እቸገራለሁ፡፡ የህትመት፣ ኤሌክትሮኒክስና ማህበራዊ ሚዲያው ግድቡ ያለበትን ደረጃ በትክክል ለህዝብ በማሳወቅ ላይ ክፍተት አለ፡፡ ብዙ ዘገባዎች ቢሰሩም አሁን ከሚገኝበት አፈጻጸም አኳያ ህዝብ በደንብ እንዲያውቀውና የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣ በማድረግ ቀሪ ሥራዎችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ውስንነት አላቸው » ብሏል፡፡
እንደ ወጣት በረከት ገለጻ፤ መገናኛ ብዙሃን በህዝብ ዘንድ ትልቅ አቅም መፍጠር ስለሚችሉ ወቅትንና ሰዓትን ሳይጠብቁ መረጃዎችን  ለህዝብ ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በማንኛውም ሰው ላይ የሚኖረው የተለያየ የፖለቲካ አመለካከትና አቋም አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መንፀባረቅ የለበትም፡፡ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ህዝብ እንጂ የማንም ሊሆን አይችልም፡፡ በግድቡ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት አላስፈላጊ ወሬዎችን የሚያሰራጩ ሚዲያዎችና ግለሰቦች ተገቢ ተግባር አለማከናወናቸውን መረዳት ይገባቸዋል፡፡ አሉታዊ ወሬ ማሰራጨታቸው በግድቡ ላይ ምንም የፈጠረው ተጽዕኖ የለም፤ ወደፊትም ይፈጥራል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሆኖም ከድህነት ለመውጣት የሚደረገውን ትግል ሊያግዝ የሚችል ፕሮጀክት በመሆኑ አገራዊ አጀንዳ ላይ አንድ መሆን ተገቢ ነው፡፡  
«በግድቡ ላይ ኢጋድን ጨምሮ ታላላቅ ተቋማት ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡ ግድቡ በፍጥነት ተጠናቅቆ ወደ ተሻለ ደረጃ ለመድረስ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ዜጎች አሻራቸውን ማስቀመጥ አለባቸው፤ የሚችሉ በገንዘብ የማይችሉ በሃሳብ መደገፍ ይገባቸዋል፡፡» በማለትም ወጣት በረከት መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡
«በግድቡ ላይ ሁሉም ዜጋ እኩል ሚና ያለው በመሆኑ ሁሉም በተሰማራበት ሙያ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያሉ ሰዎች ትክክለኛ መረጃ ለህዝብ በማቅረብ አገራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ ግድቡ በተገቢው ሁኔታ እየተሰራ ቢሆንም ከዚህ አኳያ የመንግሥትም ሆነ የግል ሚዲያዎች ለህዝብ ከማሳወቅ ላይ ኃላፊነታቸውን አልተወጡም፡፡ ተገቢውን የማስተዋወቅ ሥራም ሰሩ ለማለት እቸገራለሁ፡፡» ያለው ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ጦማሪ የሆነው ወጣት ሰናይ አማረ ነው፡፡  
ወጣት ሰናይ እንደሚለው፤ በተለይ ሰሞኑን በግብጽና ሱዳን አለመግባባት ግብጽ ሠራዊቷን ኤርትራ ድንበር ማስፈሯን ተከትሎ በግድቡ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥሯል የሚሉ ወሬዎች ከእውነታው የራቁ ናቸው፡፡ ግድቡ በተገቢው ሁኔታ እየተገነባ ሲሆን፤በግድቡ ላይ መሰረታዊ ለውጦች አሉ፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ኮርቻ ግድቡ (ሳደል ዳም) ተጀምሮ ነበር የተመለከትኩት፡፡ በአሁኑ ወቅት ወደ መጠናቀቁ መድረሱን ተመልክቻለሁ፡፡ የግድቡ ግንባታና ተርባይኖች እየተጠናቀቁ ያለበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህ በጣም የሚያስደስት ነው፡፡
የግድቡ ግንባታ ቀጣይነት ያለው ፕሮጀክት በመሆኑ እስኪጠናቀቅ ድረስ የአገሪቱ ዜጎች የሚያደርጉትን ድጋፍ ሊቀጥሉ ይገባል፡፡ ሁሉም ሚዲያ ክፍተቶችን በመለየትና ጥንካሬዎችን በማሳየት ግንባታው ተጠናቅቆ ፍፃሜው እውን እንዲሆን የበኩላቸውን ገንቢ ተግባር ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡

ዜና ሐተታ
ዑመር እንድሪስ

Published in የሀገር ውስጥ

∙ ዴሞክራሲ ረጅም ጉዞ እና ትዕግስት የሚጠይቅ መሆኑንም ገልጻለች
∙ ሬክስ ቲለርሰን ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ተወያይተዋል

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሠላማዊ የስልጣን ሽግግር፤ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና የህዝቡ ትዕግስት የሚደነቅ መሆኑን  አሜሪካ አስታወቀች፡፡ ዴሞክራሲ ረጅም ጉዞ እና ትዕግስት የሚጠይቅ መሆኑንም ገልጻለች።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ትናንት በሸራተን አዲስ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሬክስ ቲለርሰን ኢትዮጵያ ለሠላማዊ የስልጣን ሽግግር የሰጠችው ትኩረት ዓርአያ በመሆኑ አሜሪካ በአዎንታ የምትመለከተው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲ ግንባታ ጀማሪ በመሆኗ በአሁኑ ወቅት በመንግሥት በኩል የተጀመሩ ጥረቶች እንደሚበረታቱ፤ አሜሪካም ከኢትዮጵያ ጋር በስፋት ለመስራት ዝግጁ መሆኗን አስገንዝበዋል፡፡
ዴሞክራሲ ረጅም ጉዞ እና ትዕግስት የሚጠይቅ እንደሆነ የገለፁት ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን፤ በአገሪቱ የተከሰቱ ችግሮችንም በአግባቡ ለመቆጣጠርና ወደ መደበኛው መስመር ለመመለስ የተጀመረው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
 ሕዝቡ ሠላማዊ የስልጣን ሽግግር ለማከናወን በትዕግስት እየተጠባበቀ በመሆኑ ትልቅ አድናቆት እንደሚሰጠው፣ የሚመራቸውን መንግሥት መምረጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ድርሻ መሆኑን፤በሁከትና ብጥብጥ ግን የሚመጣ ለውጥ ሊኖር እንደማይገባ  ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡
ሬክስ ቲለርሰን ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ በሱዳንና ደቡብ ሱዳን መካከል ሠላም በማስከበር እንዲሁም በሶማሊያ እና በሌሎች የአፍሪካ አገራት ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በምትጫወተው ሚና ቀዳሚውን ድርሻ የምትይዝ በመሆኗ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጣት አገር ናት ብለዋል፡፡  
በኢትዮጵያ ሠላም እና ብልጽግና እንዲሰፍን የአሜሪካም ፍላጎት በመሆኑ ድጋፋችን አይነጥፍም ያሉት ሚኒስትሩ፤ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መሆኑን ፤ የሁለቱ አገራት ትስስርም ወደ ላቀ ምዕራፍ እንዲሸጋገር አሜሪካ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በበኩላቸው፤ ሁለቱ አገራት ከአንድ መቶ ዓመት የዘለለ ሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፤ በቀጣይ በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባው ወዳጅነት እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡ አገራቱ በማህበራዊ፤ በምጣኔ ሀብታዊና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መሥራታቸውን እንደሚቀ ጥሉም አክለው ገልፀዋል፡፡
በተያያዘ ዜና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን  በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሁለትዮሽ እንዲሁም በአህጉሩ ጉዳዮች ዙሪያ የተወያዩ ሲሆን፤ሁለቱ አገራት በልማት፣ በፀጥታ፣ በሰላምና በፀረ ሽብር ትግል የሚያደርጉትን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉና  በአፍሪካ ቀንድ  በፀጥታ ጉዳይ ላይም  በጋራ እንደሚሰሩ ተወያይተዋል።

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

Published in የሀገር ውስጥ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሁለት ሶስተኛ አብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡ በዛሬው እትማችን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስመልክቶ የሰጡትን ማብራሪያ እንዲሁም የተነሱትን አስተያየቶችና ጥያቄዎች ይዘን ቀርበናል፡፡
አቶ ጌታቸው እንዳብራሩት፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በዋናነት ሕገመንግስቱንና ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎችን ለመከላከል የወጣ ነው፡፡ ይሄን አዋጅ ለማውጣት መሰረታዊ የሆኑ ምክንያቶች አሉ፡፡ እንደሚታወቀው በሕገመንግስቱ በግልፅ እንደተቀመጠው አንድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው መሟላት የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ ነው፡፡ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተው ሲገኙ ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደሚታወጅ ሕገመንግስቱ በግልጽ ይደነግጋል፡፡
በዚህም መሰረት አንደኛው የውጭ ወረራ ሲያጋጥም የሚታወጅ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና ይሄም አደጋ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት መከላከልና መቋቋም የማይቻልበት ሁኔታ ሲያጋጥም የሚታወጅ ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ማንኛውም አይነት የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥምና አደጋውን ለመከላከል የሚያስቸግሩ ሁኔታዎች ሲኖሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊታወጅ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ በአራተኛ ደረጃ ደግሞ የሕዝብ ጤንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉና በሽታዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ የፌዴራል መንግስት የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደሚደነግግ ያስቀምጣል፡፡
ይሄ የተደነገገው አዋጅም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በስራ ላይ ካለ በ48 ሰዓት ውስጥ አቅርቦ እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል፡፡ በስራ ላይ ካልሆነ ደግሞ በ15 ቀናት ውስጥ አቅርቦ ያፀድቃል፡፡ ይሄ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተለይም ሕገመንግስቱንና ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ ጉዳዮች በመከሰታቸውና ይሄንንም በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት መሸፈንና መቋቋም በማይቻል ደረጃ ላይ ስለደረሰ የታወጀ አዋጅ ነው፡፡
ስለዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሕገመንግስታዊ ሥርዓት ያለውና በሕገመንግስቱ መሰረት እንዲታወጅ የተደረገ መሆኑን የተከበረው ምክር ቤት ግልፅ ግንዛቤ እንዲይዝበት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ተነስቶ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊ ያደረጋቸው መሰረታዊ ምክንያቶች ምንድናቸው የሚሉትን ጉዳዮች አንድ በአንድ ለመዘርዘር እሞክራለሁ፡፡
የመጀመሪያው ጉዳይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰተው ህገ መንግስቱን እና ህገ መንግስታዊ ሥርዓትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች እየተከሰቱ ነው፡፡ የህዝቦቻችንን እና የሀገራችንን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች የተለመዱ በሚመስል መንገድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ እና አድማሳቸው እየሰፋ የሄደበት ሁኔታ እየተከሰተ መጥቷል፡፡ በዚህም የተነሳ በህገ መንግስቱ እውቅና ያገኙ እና ህገ መንግስታዊ ዋስትና የተሰጣቸው መብቶች ዜጎች እንዳይጠቀሙባቸው የደረሱበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
ዜጎች በፈለጉበት የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቦታ ወደ ቦታ ተዘዋውረው በነጻነት የመስራት እና መንቀሳቀስ የሚችሉበት ሁኔታዎችን የሚገድቡ ልምዶች እና እንቅስቃሴዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየታየ ነው፡፡ በሌላ በኩል ማንኛውም የሀገሪቱ ዜጋ በፈለገበት የሀገሪቱ ክልል እና ቦታ የመኖር ከዚያም ባለፈ ሀብት የማፍራት እና በሀብቱ የመጠቀም እድል የሚገድቡ እንቅስቃሴዎች እየሰፉ የመሄዳቸው ጉዳይ ህገ መንግስታዊ ሥርዓት ላይ የተቀመጠውን ዋናውን እና መሰረታዊ መብቶች ዜጎቻችን በአግባቡ ማጣጣም በማይችሉበት ደረጃ ላይ የሚያደርሱ እንቅስቃሴዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መምጣታቸው እና አድማሳቸው እየሰፋ የመጣበት ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ ጉዳይ ነው፡፡
በሌላ በኩል በቅርብ ጊዜ የሚታየው በተለያዩ የሁከት እና የብጥብጥ ሀይሎች እንቅስቃሴ እና ባደረጉት ቅስቀሳ የመንግስት አገልግሎቶች የሚስተጓጎሉበት በሌላ በኩል የግሉ ዘርፍ እንቅስቃሴዎች የተገደቡበት በዚህም የተነሳ ህብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ ለመግባት በማይችልበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ የሚያደርጉ ሁኔታዎች እየተከሰቱ መጥተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ የሚገደብበት፤ ህብረተሰቡ መሰረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት የሚያስችሉ ሸቀጦችን በአግባቡ የማያገኝበት በሌላ በኩል በሰላም ወጥቶ በሰላም የማይገባበት ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ማስታወስ ይቻላል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ አሁን አሁን ላይ እየተከሰቱ ያሉት ሁከት እና ብጥብጦች ሀይል የተቀላቀለባቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሰው ህይወት ላይ ጥቃት የማድረስ ጉዳይ የተለመደ ተግባር በሚመስል ደረጃ የሚታይባቸው ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡
የንብረት መውደም እና አሁንም ቢሆን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ላይ መጥፎ ጠባሳ የሚጥሉ እንቅስቃሴዎች ተፈጥረዋል፡፡ የህዝቦች መፈናቀል እና በፈለጉበት አካባቢ የመኖር እድላቸውን የሚዘጋ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ መንገድ መዝጋት፣ የአገልግሎት ተቋማት እንዲዘጉ የማድረግ እና በተለይም በከተሞች አካባቢ ህገ ወጥ የመሬት ወረራ እና የህግ የበላይነትን የሚጥሱ እንቅስቃሴዎች እየሰፉ እንዲሄዱ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡
እነዚህ ተዳምረው በሚታዩበት ጊዜ ችግሩ እየዋለ እያደረ በሄደ ቁጥር የብጥብጥ ሀይል እየገነነ እና ህጋዊ ሥርዓት እየተጣሰ በአንጻሩ ደግሞ ህገ ወጥነት የበላይነት እያገኘ የሚሄድበት ሁኔታ እየተንሰራፋ መጥቷል፡፡ ብሄርን መሰረት ያደረገ ጥቃት እና የዜጎች መፈናቀል ተከስቷል፡፡ የሀገራችን ኢኮኖሚ ክፉኛ የተጎዳበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ህዝቡ በሰላም ወጥቶ በሰላም የማይገባበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ተዳምረው ሲታዩ ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱ ላይ የተቃጡ አደጋዎች እና ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በአግባቡ ማስቀጠል በማይቻልበት ደረጃ ላይ ሊያደርሱ የሚችሉ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች እየተከሰቱ በመምጣታቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጁን የሚኒስትሮች ምክር ቤት አምኖ እና ፈቅዶ በዚህ መሰረት የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲደነገግ በጋራ ውሳኔውን አሳልፏል፡፡
በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተካተቱት ጉዳዮች አምስት ክፍሎች እና 18 አንቀጾች አሉት፡፡ ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመጀመሪያው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በይዘት ተቀራራቢነት እና ተመሳሳይነት ያለው ጉዳይ ቢሆንም በዋና ዋና ጉዳዮቹ ላይ ግን የተወሰኑ መሻሻሎች እና ጭማሪዎች አሉ፡፡ በክፍል አንድ ላይ በግልጽ የተቀመጠው የአዋጁ ስያሜ እና ትርጉም የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ተቀምጠዋል፡፡ የተፈጻሚነት ወሰኑን በምናይበት ጊዜ በመላ ሀገሪቱ ተግባራዊ የሚደረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሆኖ ተደንግጓል፡፡
በክፍል ሁለት የተቀመጡት በአስቸኳይ ጊዜ የሚወሰዱ እርምጃዎች ናቸው፡፡ በዚህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚወሰዱ እርምጃዎች ከባለፈው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር ለየት ከሚያደርጉ ጉዳዮች በአሁኑ ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ለመጣል ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች በዋናነት በጠንሳሽነት እና በማቀድ በነዚህ ተግባራት የሚፈጸሙ እንቅስቃሴዎች ሲያደርጉ የነበሩ አካላት በዋነኛነት ተጠያቂ የሚሆኑበት ሁኔታ የሚያካትት መሆኑ አንዱ ለየት የሚያደርገው ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም በሌሎች ግፊት ለተለያዩ የሁከት እና ብጥብጥ የሚሳተፈው ሀይል ብቻ ሳይሆን በዋነኛነት ማተኮር ያለብን ይህንን አቅደው ጠንስሰው እንዲተገብሩ በሚያስገድዱ አካላት ላይ እንዲሆን እና ችግሩን ከስር መሰረቱ መፍታት የሚያስችል እንቅስቃሴ ማድረግ የምንችልበት እንዲሆን ተደርጎ ነው የተቀረጸው፡፡
ሁለተኛው ካለፈው ለየት የሚለው አሁን ላይ የተፈጠረው ሁከት እና ብጥብጥ ካስከተላቸው ጉዳዮች አንዱ አደጋ ሆኖ የሚታየው ብሄር ተኮር የሆኑ ጥቃቶች እንዲሁም መፈናቀል አጋጥሟል፡፡ ስለዚህ ከቀዬቸው የተፈናቀሉ ዜጎቻችንን ወደ ነበሩበት ቦታ ለማቋቋም መንግስት የሚያደርገውን ጥረት ማገዝ እና መደገፍ አንዱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያተኩርበት እና ካለፈው ያልተካተተ ወይንም መካተት አለበት ተብሎ የገባ አዲስ አንቀጽ ነው፡፡
ህዝባዊ አገልግሎት የሚካተትባቸው ተቋማት ውስጥ አሁን አሁን የሚታዩ ክፍተቶች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የሁከትና የብጥብጥ መነሻ እየሆኑ ብሔር ተኮር የሆኑ ግጭቶችን የሚያሳትፉበት ሁኔታ አለ፡፡ እነዚህን መከላከል የሚያስችል ሥራ መስራትና በየአካባቢው የሚፈጠሩ ሁኔታዎችን የማስተካከል ስራ መሰራት እንዳለበት የተጨመረው አንቀጽ ያሳያል፡፡ ሁከትና ብጥብጡን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ውስን የሆነውን የአገሪቱ የመሬት ሀብት ላይ የሚደረግ ህገ ወጥ የመሬት ወረራ አለ፡፡ ህገ ወጥ የመሬት ወረራና ህገ ወጥ ግንባታዎች እንዲቆም የማድረግ እና በህግ የሚመራ የመሬት አሰጣጥ ሥርዓት የተስተካከለ እንዲሆን አስተዳደሮችን የማገዝና የመደገፍ ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡ በኢንቨስትመንት ላይ የተሰማራውንም ከአደጋና ከጥቃት መከላከል የሚቻልበትን ሁኔታ የመፍጠር እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው ከተከለከሉት እርምጃዎች ውስጥ አዲስ የተካተተ ነው፡፡
ቁጥር ሶስት ላይ የሚመለከቱት ሁኔታዎች የኮማንድ ፖስቱና የመርማሪ አካላትን የሚያቋቁም ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩት አካላት ላይ የተጨመሩት የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርም የኮማንድ ፖስቱ አካል ሆነው እንዲቀጥሉ ማድረግ ነው፡፡ ኮማንድ ፖስቱ ወደ ታች የሚደራጅበት መልክ ያለው ሲሆን፤ የፌዴራል መንግስት ዋነኛው የበጀት ምንጭ ሆኖ ያገለግላል፡፡ በህግ አስከባሪ አካላት ስምሪት ውስጥ ስለሚገቡ እነዚህን ለመደገፍ ክልሎች ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ በመርማሪ ቦርዱ በህገመንግስቱ ላይ የተቀመጡ ስልጣንና ተግባራት በዝርዝር ተቀምጧል፡፡ እነዚህም የሰብዓዊ መብት ጥሰት እዳያጋጥም ልዩ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ሰባት አባላት ያሉት መርማሪ ቦርድ ይኖራል፡፡
በክፍል አራት ላይ የተጨመረው የመከላከል፣ የምርመራ፣ የክስና ፍርድ ሂደትን የሚመለከት ነው፡፡ ባለፈው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም የፖለቲካ አመራሩ ለጸጥታ ኃይሉ ስራዎችን በመስጠት የዳር ተመልካች የሚሆኑባቸውን እንቅስቃሴዎች የነበሩበት በመሆኑ ይህንን ማስተካከል እንዲቻል በየደረጃ የሚገኙ የደህንነት ምክር ቤቶች ሚና ምን እንደሆነ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ምክር ቤቶቹ የፖለቲካ ስራውን የመምራት፣ ህዝብን የማነቃነቅና አጠቃላይ የኮማንድ ፖስቱን ተልዕኮዎች የማገዝና የማስፈጸም ኃላፊነት እንዳለባቸው በግልጽ የተቀመጠበት ሁኔታ አለ፡፡ የአገር መከላከያ ሰራዊትም በህገመንግስቱ አንቀጽ 87 ንኡስ አንቀጽ ሁለት የተሰጠውን ተልዕኮ የሚያስፈጽምበት አንቀጽ ተጨምሯል፡፡ የሚያዙ ሰዎችን ፈጣን ምርመራ፣ የክስ ሂደትና በፈጣን ፍርድ እዲያገኙ የሚሰሩ በየደረጃው የፖሊስ እና ፍርድ ቤቶች ልዩ አስተዳደሮች እንዲኖሩ ለማድረግ የተሞከረበት ገጽታ ነው፡፡ ሌሎች የነበሩ ድንጋጌዎች በፊተኛው የአዋጅ ድንጋጌ ላይ እንደነበሩ ሆነው እንዲቀረጹ ተደርጓል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬ ያቀረቡትን ማብራሪያ ተከትሎ ከምክር ቤት አባላት ጥያቄና አስተያየት ተሰንዝሯል፡፡ የመጀመሪያ አስተያየት ሰጪ የመሬት ወረራንና ህገ ወጥ ግንባታን የሚመለከተውን እጋራለው ብለዋል፡፡ በተጨማሪ በሰጡት አስተያየት እንዳሉት፤ መሬትን የመቀማትና የመመለስ ተብሎ የተካተተው ላይ ግን መስተካከል አለበት የምለው ክልሎች የራሳቸው የሆነ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ስላላቸው የራሳቸው አሰራርም ስላላቸው ግልጽ በሆነ ቋንቋ ቢቀመጥ የሚል ነው፡፡ ኢንቨስትመንትን የሚያስተጓጉል ስራቸውን በሚሰሩበት ጊዜ ተጽዕኖ የሚፈጥር ነገር ካለ በመተባበር ደህንነትን መጠበቅ ይቻላል ግን ኢንቨስትመንትን መውሰድና አለመውሰድ በየክልሎቹ የአሰራር መሰረት ቢሆን መልካም ነው፡፡
የክልል መንግስታት በጀትን ይመድባሉ የሚለው አሻሚ በመሆኑ በጀትም ላይኖር ስለሚችል ግልጽ በሆነ ቋንቋ ቢቀመጥ፡፡ የኮማንድ ፖስት አደረጃጀት አስመልክቶ ከበፊቱ የኮማንድ ፖስት ሪፖርት በቀረበው መሰረት ተናቦ ባለመስራት የተከሰቱ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡
የኮማንድ ፖስት አደረጃጀትን አስመልክቶ ቀደም ሲል የተቀመጡ ነገሮች አሉ በጋራ ባለመስራት የተከሰቱ ችግሮች አሉ፡፡ በየደረጃው ያለው የአስተዳደር አካል በኮማንድ ፖስቱ ሚናው በትክክል መቀመጥ አለበት፡፡ ከዚህ ቀደም የዞን አስተዳደር የኮማንድ ፖስቱ አባል አልነበረም፡፡ ግን የዞኑን አጠቃላይ የጸጥታ ጉዳይ ይመለከተዋል፡፡ የአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታ፣ ባህል አናኗሩን ስለሚያውቅ ፖለቲካዊ አመራረር በመስጠት የተሻለ ውጤት ያስመዘግባል፡፡ በተወከልንበት ምስራቅ ወለጋ ነቀምት የሃይማኖት አባቶች አመራሩ ግጭት እንዳይከሰት ይሰራል፡፡ በአሁንም ግጭት ምንም ንብረት እንዳይወድም ተደግጓል፡፡ ይሁንና አሁን በአካባቢው የታሰሩ የዞኑ ምክትል አስተዳደርና ከንቲባው ታስረዋል፡፡ ገና ከአሁኑ ችግር እየታየ ስለሆነ የአካባው መስተዳድር እንዲፈታው መደረግ አለበት፡፡
ሁለተኛው የምክር ቤት አባላት በሰጡት አስተያየት፤ በአዋጁ ላይ በአንቀጽ ሁለት ስር ከተቀመጡት ቁጥሮች ውስጥ ሶስት ቁጥር ላይ፤ ህግ በሚለው ትርጉም ላይ ህግ ማለት የፌዴራል ህገመንግስት እንደ አግባብነቱ የፌዴራል እና የክልል ህዝቦች ተፈጻሚነቱን እያስቀመጠ ስለሆነ ያለው እንደ አግባብነቱ የሚለው ቃል ከዚህ ውስጥ ቢወጣ። ህገመንግስቱ ለፌዴራል እና ለክልል ህጎች ተፈፃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ የሚያመላክት ሁኔታ ቢቀመጥ የሚል ሃሳብ አለኝ ብለዋል።
በተጨማሪም በሰጡት አስተያየት፤ በአንቀጽ አራት ንኡስ ቁጥር አንድ ማንኛውም ሁከት ብጥብጥ እና በህዝቦች መካከል መጠራጠር እና መቃቃርን ይፋዊ የሆነ የድብቅ ቅስቀሳ ማድረግ እንደማይቻል ተቀምጧል። ከዚህ ውስጥም ይፋዊ የድብቅ ቅስቀሳ ማድረግ የሚለው ቃል በራሱ አሻሚ ነው። ይፋዊ ከሆነ ይፋዊ ነው። የድብቅ ከሆነ ይሄንን በግልጽ በማስረጃ አስደግፎ ለማቅረብ ስለማይቻል፤ የድብቅ ቅስቀሳ የሚለው ከዚህ ውስጥ ቢወጣ የሚል ሃሳብ አለኝ። በዚሁ አንቀጽ ንኡስ ቁጥር ሶስት ፤በቡድን ሆኖ መንቀሳቀስን ይከለክላል ይላል። በቡድን ሆኖ መንቀሳቀስ ማለት ምን ማለት ነው? ይሄ የራሱ የሆነ ማብራሪያ እና ትርጓሜ ሊሰጠው ይገባል። በዝርዝር ሁኔታዎቹ መቀመጥ ካልቻለ በአሁኑ ወቅት የትኛውም የማህበረሰባችን ክፍል ካለው የባህል መስተጋብር አኳያ እንቅስቃሴው በቡድን ነው። ለምሳሌ ወደ ገበያ፣ታዳጊዎች ወደ ትምህርት ቤት ወዘተ የሚሄዱት በቡድን ነው። ይሄ ሁኔታ ስላለ ትርጓሜው በዝርዝር ተብራርቶ ሊቀመጥ ይገባል።
በንኡስ ቁጥር አራት ላይ ደግሞ፤ ማንኛውንም ሰው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ስር እንዲውል ያደርጋል የሚል ተቀምጧል። ይሄ አንዳለ ሆኖ በአስቸኳይ ወደ ፍርድ ቤት የሚሄድበት ሁኔታ ስለመኖሩ ምንም የተቀመጠ ነገር የለም። በህገ መንግስቱ ግን አንድ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ከዋለበት በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ አለበት ይላል። ከዚህ አንጻር ሲታይ ይህ ክልከላ ትንሽ ለቀቅ የተደረገ ይመስላል። ምናልባትም ለቀቅ ማድረግ አስፈልጎም ከሆነ፤ ተጠርጣሪው በአስቸኳይ ወደ ፍርድ ቤት መቅረብ የሚችልበት ሁኔታ መቀመጥ አለበት።
በዚሁ አንቀጽ ንኡስ ቁጥር አስራ አንድ ፤የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ያቋቁማል የሚል የተቀመጠ ነገር አለ። ይሁንና መልሶ በሚያቋቁምበት ጊዜ የተፈናቀሉ ወገኖችን ፍቃድ መጠየቅ አስፈላጊ ነው። የተፈናቀሉበትን ክልል መንግስት በማነጋገር በመመካከር የሚሰራ መሆኑን አብሮ ቢካተት የተሻለ ነው የሚል ሃሳብ አለኝ።
ንኡስ ቁጥር 15 ላይ ደግሞ፤ ከኢንቨስተሮች ማፈናቀል በተመለከተ በህገመንግስቱ አንቀጽ 25 «በህግ ፊት ሁሉም እኩል ነው» ይላል።ከዚህ አኳያ ሁኔታውን ስንመለከተው ኢንቨስተሮችን ብቻ ለይቶ እንደማውጣት ነው። በሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ የሚደርሱ አንዳንድ ጉዳቶችን በዛ ውስጥ አካቶ መስራት እንዳይቻል ህግ ማበጀት ይሆናል። ስለዚህ ኢንቨስተሮችን ብቻ ለይቶ ማውጣት ተገቢ አይሆንም። ይህ መታየት ይገባዋል።
በአንቀጽ ስድስት ንኡስ ቁጥር አንድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ስለሚያስፈጽመው ኮማንድ ፖስትን የሚመለከት ነው። እዚህ ላይ እንደተቀመጠው የኮማንድ ፖስቱ አባላት የፌዴራል መንግስት አባላት ናቸው።ይሁንና ግን ችግሮቹ ባሉበት ክልሎች ላይ ያለ የክልሉ መንግስት ፕሬዚዳንት የዚህ የኮማንድ ፖስቱ አባል ሆኖ የሚሰራበት ፣ የሚያግዝበት ሁኔታ መኖሩ እጅግ አስፈላጊ ስለሆነ በዚህ ውስጥ መካተት አለበት የሚል ሃሳብ አቅርበዋል።
ከዚሁ በተመሳሳይ በንኡስ ቁጥር ሁለት ላይ፤ የህግ አስከባሪ አካላትን በአንድ እዝ ስር አድርጎ በበላይነት ይመራል ይላል። ከህግ አስከባሪ አካላት ውስጥ አንደኛው የፖሊስ ኮሚሽን ነው።ይህ የፖሊስ ኮሚሽን ደግሞ በፌዴራል እና በክልል ስር አለ። በዚህ ንኡስ ቁጥር ላይ ሲቀመጥ የክልል መስተዳድርን መሰረት ባደረገ መልኩ አይደለም። ስለዚህ ይሄንን መሰረት ቢያደርግ የተሻለ ነው የሚል ሃሳብ አለኝ።
በአንቀጽ 12 ንኡስ ቁጥር አንድ ላይ የምርመራ እና የክስ ሂደትን በተመለከተ በፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ እና በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እንደሚሰራ ተቀመጧል። ከአገሪቱ የቆዳ ስፋት እና ጠቅላላ ካለው የስራ ብዛት ብሎም ጫና ተነስተን ለፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ እና ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ብቻ ይሄንን ስራ መተው አጅግ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል። ውሳኔዎችም በተገቢው ጊዜ እንዳይሰጡ የሚያደርግ ነው። የፍትህ ሥርዓቱን ተጎታች የሚያደርግበት ሁኔታ ይኖራል የሚል ስጋት አለኝ። ህገ መንግስቱ ለፌዴራል እና ለክልል መንግስታት በተሰጠው ስልጣን መሰረት ከፍርድ ቤቶች ጋር የተሰጠው ስልጣን እንዳለ ሆኖ ፤ ነገር ግን የፌዴራል አቃቤ ህግ ከጎን እገዛ የሚያደርግበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። የራሱ በራሱ ክልሉ በህገ መንግስቱ የተሰጠውን ስልጣን የሚተገብርበት ሁኔታ መፈጠር አለበት እንጂ፤ ለፌዴራል አቃቤ ህግ እና ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ብቻ መስጠቱ ስራውን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማስኬድ አዳጋች የሚያደርገው ይሆናል።
በአዋጁ ማብራሪያ ገጽ ስምንት ላይ ፤ ኮማንድ ፖስቱ እንደ አስፈላጊነቱ በተዋረድ ተመሳሳይ የኮማንድ ፖስት ይዘረጋል ይላል።ይህ በአዋጁ ውስጥ የለም። በየክልሉ ያለውን ችግር በቅርብ ሆኖ ለመከታተል እና ለመፍታት ክልሎችን ያማከለ የኮማንድ ፖስት ሥርዓት ቢፈጠር የተፈጠረውን ችግር ትክክለኛውን መፍትሄ መስጠት ያስችላል። በአዋጁ ውስጥ ቢካተት የሚል ሃሳብ አለኝ።
በክፍል ሁለት አንቀጽ አራት ላይ በኮማንድ ፖስቱ የሚወሰዱ እርምጃዎችን በተመለከተ በንኡስ ቁጥር 7 ፤ ኮማንድ ፖስቱ የአገልግሎት መስጫ ተቋማቱ እንዲዘጋ ያዛል ይላል። ወረድ ብሎ ደግሞ በንኡስ ቁጥር 12 ላይ የአገልግሎት መስጫ ተቋማቱ የሚያስተጓጉሉ ችግሮችን ጥበቃ ያደርግለታል ይላል። እነዚህ ሁለቱ ሃሳቦች እርስ በዕርሳቸው የሚጣረሱ ናቸው። ስለዚህ በንኡስ ቁጥር ሰባት ላይ የተቀመጠው ሃሳብ ቢወጣ የሚል ሃሳብ አለኝ። አልያም የትኞቹ የአገልግሎት ተቋማት ናቸው የሚዘጉት የሚለው በማብራሪያ ሊቀመጥ ይገባዋል ባይ ነኝ።
ይቀጥላል

Published in ፖለቲካ

ቁጥሩ 202 የሚደርስ የሰው ኃይል ይዞ አገልግሎት በመስጠት ላይ በሚገኘው ቃሊቲ ደረቅ ወደብ ተርሚናል ጽህፈት ቤት ጊቢ ውስጥ ነን፡፡ የጽህፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንዴ ታደገ ባደረጉልን ገለፃና እኛም ተዘዋውረን እንዳየነው በወደቡ መልካም የሚባሉ ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡
እንደ አቶ ወንዴ ገለፃ ከጥቂት ጊዜያት በፊት በነበረው አሰራር የወጭ ንግድ አገልግሎትን ለማከናወን ባዶ ኮንቴይነርና የሚታሸገው ዕቃ ደግሞ በሸራ ታስሮ ለየብቻ ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ ወደብ ይላካል፡፡
የማሸጉ ሥራ የሚከናወነው ጅቡቲ ወደብ ላይ ነው፡፡ በዚያው ወደ ውጭ ይላካል፡፡ ለአገልግሎቱም በአንድ ኮንቴይነር እስከ 20 ዶላር፣ ለጉልበት 60 ዶላር በድምሩ ከ80 ዶላር ያላነሰ ይከፈላል፡፡ እንዲህ ያለው አሰራር ሀገሪቷን ለወጪ ብቻ ሳይሆን፣ ለትችትም ዳርጓታል፡፡ የማሸጉን ተግባር በሀገር ውስጥ ማከናወን እየተቻለ ሥራውን አሳልፎ መስጠቱ ዜጎችንም የሥራ ዕድል አሳጥቷል፡፡
አቶ ወንዴ እንዳሉት ባዶ ኮንቴይነርና እንደቡና፣የቅባት እህልና ጥራጥሬ የመሳሰሉት የወጭ ንግዶች በሸራ ለየብቻ በሚላኩበት ወቅት ለጥራት መጓደል፣ለቅሸባና ለብክነት ይዳረጋሉ፡፡ በተለይ ቡና ለባዕድ ነገሮች የመጋለጥ እድሉ ሰፊ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ የማሸጉ ሥራ በጅቡቲ ወደብ ላይ በመለመዱ እንጂ እዚህ ላለመስራት በቂ የሆነ ምክንያት የለም፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን የቆየው ልማድ ቀርቶ ቃሊቲ ደረቅ ወደብ ተርሚናል ጽህፈት ቤት ሥራውን የራሱ አድርጎታል፡፡ ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣንና ከቡና ቦርድ ጋር በደረቅ ወደቡ ላይ ታሸገው የሚላኩትን የወጭ ንግዶች በስፍራው ተገኝተው በፍተሻ እንዲያረጋግጡ ተስማምተው የማሸጉ ሥራ በወደቡ ውስጥ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ሥራው ከተጀመረ አጭር ጊዜ ቢሆንም በተለያየ መልኩ ተጠቃሚ የሚያደርግ ውጤት አስገኝቷል፡፡
የወጪ ንግዶች በሀገር ውስጥ ታሽገው መላካቸው የሚያስገኘውንም ጥቅም አቶ ወንዴ እንዳስረዱት ላኪው በአንድ ኮንቴይነር እስከ 20ዶላር የሚያስወጣው ወጪ ይቀንስለታል፡፡ በሀገር ውስጥ በአንድ ኮንቴይነር 940 ብር ብቻ ነው የሚከፈለው፡፡ ጅቡቲ ላይ አንድ ኮንቴይነር ለማሸግ ለቀናት ወረፋ ይጠበቃል፡፡ በዚህ ጊዜም የሚታሸገውን አገልግሎት ይዞ የሄደ የጭነት ተሽከርካሪ ለተጨማሪ ወጪና ለደህንነት ሥጋት ይጋለጣል፡፡ አገልግሎቱ በሀገር ውስጥ መጀመሩ በጊዜ፣ በጉልበትና በገንዘብ የሚባክነውንና የደንበኞችንም ቅሬታ ይፈታል፡፡ ወጪን በማዳን ገቢ መገኘቱና ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩ ሌላው ጥቅም እንደሆነ አቶ ወንዴ ያስረዳሉ፡፡
በተጀመረው የማሸግ አገልግሎት ለ240 የአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡«ሀሰን፣ ጌታቸው፣ በኃይሉና ጓደኞቻቸው ጫኝና አውራጅ የህብረት ሽርክና» በሚል ስያሜ ማህበር መስርተው በሥራው ላይ ከተሰማሩት መካከል የማህበሩ ሰብሳቢ ዳዊት በጋሻው እንደገለፀልን አባላቱ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ነው ወደ ሥራ የገቡት፡፡ እስካሁንም በወደቡ ውስጥ በተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የአገልግሎት ክፍያ አግኝተዋል፡፡ እያንዳንዱ አባል በክፍፍሉ ጥሩ ተጠቃሚ ለመሆን ችሏል፡፡ በማህበሩ ውስጥ የሚገኙት አባላት ቀደም ሲል በቀን ሥራ፣በጅቡቲ ወደብም ይሰሩ የነበሩና በቂ ገቢ ያልነበራቸው ሲሆኑ፣በአንድ ላይ ተደራጀተው ለመስራት አልተቸገሩም፡፡ በጅቡቲ ያከናውኑት የነበረው ሥራ ልምድ ሆኗቸው የማሸጉን ሥራ በአግባቡ እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡
በቃሊቲ ደረቅ ወደብ ተርሚናል ጽህፈት ቤት በነበረን ቆይታም በማህበር የተደራጁት ወጣቶች ኮንቴይነር ሲያጥቡና በውስጡም ካኪ ቀለም ያለው ወረቀት ሲያለብሱ አይተናል፡፡ ለቡና ማሸጊያ ነበር ኮንቴነሩን ሲያዘጋጁ የነበረው፡፡ ቡናው በባዕድ ነገር እንዳይመረዝና ቢፈስስም መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያስችል ነው ቅድመ ዝግጅቱ፡፡
የቃሊቲ ደረቅ ወደብ ተርሚናል ጽህፈት ቤትን መልካም ተሞክሮ ይዘን ወደ ገላን ደረቅ ወደብ ተርሚናል ጽህፈት ቤት አመራን «ሮሮ» በተባለ የጭነት ተሽከርካሪ ከጅቡቲ ተጭነው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች ማከማቻ ሆኖ ያገለግላል፡፡ የጽህፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታየ ጫላ ባደረጉልን ገለፃ ጽህፈት ቤቱ በጅቡቲ ወደብ ላይ አላስፈላጊ ክምችት እንዳይኖር ታስቦ ነው የተቋቋመው፡፡ ወደቡ በአንድ ጊዜ አንድሺ አምስት መቶ፤ በአመት ደግሞ 35ሺ ተሽከርካሪዎችን የማስተናገድ አቅም አለው፡፡ ተሽከርካሪዎቹ በወደቡ የሚቆዩት ለሃያ ቀናት ብቻ ነው፡፡
የጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ታዬ እንደነገሩን ወደቡ ፈተና የሆነበትና ያልተሻገረው ተግዳሮት ከጅቡቲ ወደ ወደቡ የሚደርሱ ተሽከርካሪዎች የውስጥ አካል ስርቆት ነው፡፡ ይህን ተደጋጋሚ ስርቆት ለማስቀረት ጥረቶች ቢደረጉም ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት አልተቻለም፡፡ በተለያየ ጊዜ በተደረጉ ጥናቶች ስርቆቱ መኪናውን እያሽከረከሩ በሚመጡት አሽከርካሪዎች ቢሆንም፣ችግሩ በማን እንደሚፈጠር በደንብ መፈተሽ እንዳለበትና ማረጋገጥ ይገባል፡፡
ቀጥለንም ወደ ሞጆ ደረቅ ወደብ ተርሚናል ጽህፈት ቤት አመራን፡፡ በሥፍራው ስንደርስ የፀሐዩ ንዳድ የለበስነውን ልብሳችንን አስወልቆን ነበር፡፡ ፅህፈት ቤቱ በሁለት ተሽከርካሪዎቹ በረጨው ውሃ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ አካባቢው ከሙቀት ወደ ቅዝቃዜ ተለወጠ፡፡
የሞጆ ደረቅ ወደብ በ144 ሄክታር መሬት ላይ ነው አገልግሎቱን እየሰጠ የሚገኘው፡፡ የባቡር ትራስፖርት አገልገግሎቱ ከመጀመሩ ጋር ተያይዞ ማስፋፊያዎችን ሰርቷል፡፡ የደረቅ ወደብ አገልግሎት ማማ ሆኖ ለማገልገል ሰፊ ራዕይ አንግቦ በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኝ መሆኑን የደንበኞች አገልግሎትና ዶክመንቴሽን ቡድን አስተባባሪ አቶ ደበበ አሰፋ ስለድርጅቱ በሰጡት አጭር ማብራሪያ ገልፀውልናል፡፡
አቶ ደበበ እንዳብራሩት የሀገሪቷ የገቢ እቃዎች 72 በመቶ ያህሉ በሞጆ ደረቅ ወደብ የሚስተናገድ ነው፡፡ በአንድ ጊዜም 17 ሺ ኮንቴነሮችን የመያዝና 240 ኮንቴነሮችን የማስፈተሽ አቅም ፈጥሯል፡፡ ለሥራ አስፈላጊ በሆኑ ዘመናዊ መሳሪያዎች የታገዘ አገልግሎት መስጠት ደረጃ ላይም ደርሷል፡፡ የጉምሩክና ቀረጥ ታክስ ሥራም በዚያው ይጠናቀቃል፡፡ በቢሮ 16 ሰአት፣በተርሚናል ላይ ደግሞ 24 ሰአት በመስራት ለአገልግሎት ዝግጁ የሆነ ተቋም መሆኑም ተገልጿል፡፡ ሞጆ ደረቅ ወደብ አገልግሎቱን በድንኳን ጀምሮ ዛሬ ላይ መድረሱንም ነግረውናል፡፡
በያዝነው አዲስ አመት ለሞጆ ደረቅ ወደብ ተርሚናል ጽህፈት ቤት አዲስ የሆነው ሥራ በባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት መጀመሩ ነው፡፡ የጽህፈት ቤቱ ተወካይ አቶ አክሱማይት ተክለማርያም እንደገለፁልን በባቡር ትራንስፖር ከጅቡቲ ወደብ ማጓጓዝ ከተጀመረ እስካሁን 37 ጊዜ ምልልስ ተደርጓል፡፡ በእያንዳንዱ ምልልስም በአንድ ጊዜ 106 ኮንቴይነር ከጁቡቲ ሞጆ ደረቅ ወደብ ማድረስ ተችሏል፡፡ ምልልሱ በተጫነው ልክ ሲባዛ ከፍተኛ ጭነት በአጭር ጊዜ ማምጣት ተችሏል፡፡ በተሽከርካሪ የወራት ጊዜ የሚወስደው ጭነት የማመላለስ ሥራ ከስድስት ቀናት ባነሰ ጊዜ ማከናወን ተችሏል፡፡
ታዲያ በወደቡ ቆይታችን በጊቢው ተደራርበውና ተጠጋገግተው ያየናቸው ኮንቴነሮች አብዛኞቹ ለትላልቅ አገልግሎት የሚውሉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪ የተደረገባቸው ዕቃዎችን ይዘዋል፡፡ አብዛኞቹም እንደታሸጉ ወራቶችን አስቆጥረዋል፡፡ እነዚህ ባለቤት ያላቸው ግን ባለቤት አልባ የሆኑ ዕቃዎች የመንግሥት ጭምር መሆናቸው አግራሞትን ያጭራሉ፡፡
ወደብ ዕቃ ማስተላለፊያ እንጂ ማከማቻ እንዳልሆነ ወደቦቹን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ገልፆልናል፡፡ በድርጅቱ የሺፒንግ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ካፕቴን ተፈራ በዳሳ እንደነገሩን ዕቃዎቹ በወደቦቹ ላይ መቆየት ያለባቸው ጊዜ ተወስኗል፡፡ ወሰኑን አልፈው ለሚቆዩትም አስተዳደራዊ እርምጃዎች ይወሰዳሉ፡፡ ሆኖም ከአቅም በላይ የሆኑ ድርጅቶች በማጋጠማቸው በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ጫና እያሳደሩ ነው፡፡
በአጠቃላይ የድርጅቱን እንቅስቃሴ አስመልክተውም እንዳስረዱት በተለይ በቃሊቲ ደረቅ ወደብ ተርሚናል ላይ በቅርቡ የተጀመረው አገልግሎት አሽጎ በቀጥታ ወደ መርከብ ጫኙ ማድረስ የሚያስችል በመሆኑ በመካከል ላይ ይጠፋል፣ይበላሻል፣ይባክናል ከሚሉ የተለያዩ ስጋቶች ነፃ የሚያደርግ አገልግሎት ነው፡፡ አሰራሩ ዘመናዊ መሆኑም ሀገሪቷ በደረቅ ወደብ አገልግሎት የደረሰችበትን ደረጃ ያሳያል፡፡ ላኪዎች ጥቅሙን እንዲረዱት ማድረግ ላይ መስራት እንደሚገባ ካፕቴን ተፈራ ያምናሉ፡፡
እንደ እርሳቸው ገለፃ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመንና የደንበኛውን ፍላጎት ለማሟላት አሰራሩን እየፈተሸ ለማስፋት ጥረት እያደረገ መሆኑንና በተለይም በቃሊቲ ደረቅ ወደብ ላይ የተጀመረው ዕቃን አሽጎ በኮንቴይነር መላክ በሞጆ ደረቅ ወደብ ላይ በስፋት እንዲሰራ ቅድመ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡
ድርጅቱ በዋናው መስሪያ ቤትም ሆነ በደረቅ ወደብ በሚሰጠው አገልግሎት የውስጥ አቅሙን ለማጠናከር የሰው ኃይሉን በስልጠና አቅም ለመገንባት በቢሾፍቱ ባቦጋያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ «ባቦጋያ ማሪታይምና ሎጂስቲክስ አካዳሚ» በሚል ስያሜ ማሰልጠኛ ተቋም ገንብቷል፡፡ የማሪታይም ኢንዱስትሪውን ለማነቃቃት አይነተኛ ሚና እንዳለው የታመነበት ይህ የትምህርት ተቋም ዓለም አቀፍ የስልጠና መስፈርቶችን አሟልቶ ወደ ሥራ እንዲገባ በመደራጀት ላይ ይገኛል፡፡ በውጭ ሀገር የሚሰጡ ስልጠናዎችን ወደፊት በሀገር ውስጥ የመስጠት አቅምም ይፈጠራል፡፡
በውጭ የሥራ ዕድል ለሚያገኙ ዜጎች እና በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ወንዞች ክትትል እንዲኖራቸው በስልጠና በማብቃትም ድርጅቱ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል፡፡ እስካሁንም በመጀመሪያ የህክምና እርዳታ፣እራስን ከአደጋ ማዳን እንዴት እንደሚቻልና ተያያዥ ስልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን በሥፍራው ተገኝተን አይተናል፡፡ የትምህርት ተቋሙ በንድፈ ሀሳብ የሚሰጠውን ስልጠና በባቦጋያ ወንዝ ላይ በተግባር እየሰጠ መሆኑንም የትምህርት ተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች ገልፀውልናል፡፡ እስካሁንም አራት ሺ አምስት መቶ ሰልጣኞችን አሰልጥኗል፡፡
በምሥራቅ በር መውጫ ላይ የሚገኙት የቃሊቲ፣የገላንና የሞጆ ደረቅ ወደብ ተርሚናሎች የሚያከናውኑትን ተግባራት የአንድ ቀን አጭር ቆይታ አድርገን ብንቃኝም ብዙ ነገሮችን ተገንዝበናል፡፡ የሞጆ ደረቅ ወደብ ተርሚናል ለቢሮ አገልግሎት የገነባውን ለሞጆ ከተማ ማዘጋጃ አስረክቧል፣ አካባቢን በአረንጓዴ በማልማት ለጽዳትና ውበት የበኩሉን አስተዋፅኦም በማበርከቱ የልማት ሥራው አጋር ሆኗል፡፡
በገበያ ቦታዎች፣ የሸቀጥ ሱቆችና ሱፐር ማርኬቶች፣ ጎራ ብለን የምንሸምታቸው ምግብ፣ አልባሳት፣ የቤት ውስጥ ቁሶች፣ ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለግንባታና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ዕቃዎች፣ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ከጅቡቲ ወደብ ተጓጉዘው ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ስንቶቻችን እናውቅ ይሆን?

ለምለም መንግሥቱ 

Published in ኢኮኖሚ

ስድሳ ዘጠነኛው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ሬክስ ዋይኒ ቲለርሰን በአምስት የአፍሪካ አገራት የሚያደርጉትን ጉብኝት ከትናንት በስቲያ (ረቡዕ ዕለት) በኢትዮጵያ ጀምረዋል፡፡ ረቡዕ ከሰዓት በኋላ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁና በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ካሣ ተክለብርሃንን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት አቀባበል አድርገውላቸ ዋል፡፡ 

በአሜሪካውያን ፖለቲከኞች ዘንድ ከተለመዱት ድርጊቶች መካከል አንዱ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ከዋሽንግተን ዲ.ሲ ከመውጣታቸው ቀደም ብለው በመስሪያ ቤታቸው እንዲሁም በልዩ ልዩ ተቋማት (በዩኒቨርሲቲዎች፣ በጥናትና ምርምር ማዕከላት …) ተገኝተው ስለ ጉብኝታቸውና ጉዟቸው አጠቃላይ መግለጫ ይሰጣሉ፡፡
ሬክስ ቲለርሰንም ይህንኑ የአሜሪካውያን ፖለቲከኞች ልማድ አላጓደሉም፡፡ ጉብኝታቸውን በሚጀምሩበት ዋዜማ ቨርጂኒያ ውስጥ በሚገኘው ዝነኛው ጆርጅ ማሰን ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ስለ ጉብኝታቸውና ጉዟቸው ዓላማ ሰፋ ያለ ገለፃ አድርገዋል፡፡ አፍሪካ ያላት እምቅ አቅምና የአፍሪካ-አሜሪካ ግንኙነት የገለፃቸውን ሰፊ ጊዜ ወስዷል፡፡ ቲለርሰን ለጆርጅ ማሰን ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ያደረጉትን ገለፃ በአጭሩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በተለይም የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጡ ወዲህ የአፍሪካና የአሜሪካ ግንኙነት እያደገ መጥቷል፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ቢሮውን የከፈተው እ.አ.አ በ1958 የወቅቱ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ሪቻርድ ኒክሰን አፍሪካን ከጎበኙ በኋላ ነበር፡፡ በወቅቱ ጋና የነፃነት በዓሏን ስታከብር ምክትል ፕሬዚዳንት ሪቻርድ ኒክሰንን እና ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየርን ጋብዛ ነበር፡፡
ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ. ኬኔዲ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድዖ ድርጅት (USAID)ን አቋቋሙ፡፡ ከድርጅቱ የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል አንዱ የአፍሪካን ልማት መደገፍና ማጎልበት ነበር፡፡ ከዛሬ 40 ዓመታት በፊት ደግሞ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር ላይቤሪያንና ናይጀሪያን ሲጎበኙ አሜሪካ ከአፍሪካ ጋር ያላት ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ መሸጋሩን ይፋ አደረጉ፡፡
በአሁኑ ወቅት አፍሪካና አሜሪካ በፀጥታና ደህንነት እንዲሁም በኢኮኖሚ መስኮች ያላቸው ትብብር ደረጃው ከዚህ ቀደም በሁለቱ ወገኖች መካከል ታይቶ የማይታወቅና በየጊዜው እየተሻሻለ የመጣ ነው፡፡ ይህ ትብብርና ግንኙነት ደግሞ በሚቀጥሉት ዓመታትም እየጎለበተ የሚሄድ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ አህጉሪቱ በሚቀጥሉት ዓመታት የሚኖራት የሕዝብ ቁጥር እና የምታስመዘግበው ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ነው፡፡ እ.አ.አ በ2030 ከዓለም አምራች የሰው ኃይል መካከል አንድ አራተኛ የሚሆነው መገኛው ከአፍሪካ ነው፡፡ የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው ደግሞ፣ በዓለም ላይ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ አስር አገራት መካከል ስድስት የአፍሪካ አገራት ናቸው፡፡ እ.አ.አ በ2050 ናይጀሪያ ከአሜሪካ የበለጠ ሕዝብና ከአውስትራሊያ የበለጠ ምጣኔ ሀብት ይኖራታል፡፡
የዓለማችንን የወደፊት መፃኢ እጣ ፈንታና አቅጣጫ ለመረዳት ስለአፍሪካ በሚገባ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የአፍሪካ አገራት በዓለም የልማትና የደህንነት ጉዳዮች ላይ ያላቸው ሚናና አስተዋፅኦ እየጨመረ መጥቷል፡፡
የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከአፍሪካ ጋር ያለውን ግንኙነት በማጎልበት የአፍሪካ አገራት ጠንካራና ራሳቸው የቻሉ እንዲሆኑ ማድረግ ይፈልጋል፡፡ የብልፅ ጉዳይ በፀጥታና ደህንነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ሽብርተኝነት አፈፃፀሙን እያረቀቀና አድማሱን እያሰፋ በብዙ ሰዎች ሕልውና ላይ የተጋረጠ አደጋ ሆኗል፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ አደጋ በአፍሪካም ስሩን እየሰደደ ነው፡፡ እ.አ.አ በ2009 በአፍሪካ ምድር የተፈፀሙት የሽብር ጥቃቶች 300 ነበሩ፤ በ2017 ደግሞ ወደ አንድ ሺ 500 ከፍ ብሏል፡፡ የአፍሪካ አገራት ከሽብርተኞች የፀዱ እንዲሆኑ አሜሪካ ልዩ ልዩ ድጋፎችን ታደርጋለች፡፡
የአሜሪካ መንግሥት ናይጀሪያ፣ ኒጀር፣ ቻድ፣ ቤኒን እና ካሜሮን ለፈጠሩት ጥምር ግብረ ኃይል እንዲሁም ቡርኪናፋሶ፣ ቻድ፣ ማሊ፣ ሞሪታኒያ እና ኒጀር ለመሰረቱት የፀረ-ሽብር ቡድን የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፎችን ይሰጣል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አሜሪካ ላለፉት አስር ዓመታት የትራንስ-ሰሃራ ፀረ-ሽብር ትብብርን ስትደግፍ ቆይታለች፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የፀረ-ሽብር መርሃ ግብርንም እየደገፈች ትገኛለች፡፡ በአጠቃላይ አሜሪካ ለነዚህ ትብብሮች ከ140 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ አድርጋለች፡፡
የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ተልዕኮ (አሚሶም) ከአሜሪካና አፍሪካ የፀጥታና ደህንነት የትብብር መስኮች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ አሜሪካ በአፍሪካ ለሚከናወኑ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የአቅም ግንባታ ስራዎችን በማከናወን የሚወዳደራት የለም፡፡ ባለፈው ዓመት አሜሪካ ከ27 የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ 27ሺ አፍሪካውያን ሰላም አስከባሪዎችን ደግፋለች፡፡ ከአስር ዓመታት በፊት በአህጉሪቱ ውስጥ በሚከናወኑ የሰላም ማስከበር ተግባራት ላይ ተሳትፎ የነበራቸው አፍሪካውያን ሰላም አስከባሪዎች 20 በመቶ ብቻ ነበሩ፤ አሁን ይህ አሃዝ ወደ 50 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡
አሜሪካ ለፀጥታና ደህንነት ችግሮች የተሻሉና አስተማማኝ (ዘላቂ) የሆኑ መፍትሄዎችን መፈለጓ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በግጭቶች ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የምትሰጠውንም ድጋፍ ዓለም ሁሉ የሚያውቀው ነው፡፡ ይህም አሜሪካ በዓለም ላይ ግንባር ቀደሟ የሰብዓዊ እርዳታና ድጋፍ አቅራቢ እንድትሆን አስችሏታል፡፡ ዛሬ አሜሪካ በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በኢትዮጵያና በቻድ ሃይቅ ተፋሰስ አካባቢዎች በድርቅ፣ በረሃብና በግጭት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው አካላት የሚውል የ533 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ እርዳታ መስጠቷን ይፋ አደርጋለሁ፡፡
የዓለምን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የጣለችው ሰሜን ኮሪያ ወደ ድርድር እንድትመጣ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የአፍሪካ አገራት ሚና እንዲኖራቸው በትብብር እንሰራለን፡፡ እስካሁን በዚህ ረገድ አንጎላ፣ ሴኔጋልና ኢትዮጵያ ጥሩ ጅምር አሳይተዋል፡፡ ሌሎቹ የአፍሪካ አገራትም የእነዚህን አገራት ፈለግ በመከተል በሰሜን ኮሪያ ላይ ጫና ሊያደርጉ ይገባል፡፡
የአፍሪካን ምርቶች በአሜሪካ ገበያዎች ተፈላጊና ተወዳዳሪ ለማድረግ የተነደፈው የ(አጎአ)ገበያ ላለፉት 20 ዓመታት አሜሪካ በአፍሪካ ገበያዎች ውስጥ የምታደርገው የንግድ እንቅስቃሴ ፖሊሲ ዋና መሰረት ሆኖ ቆይቷል፡፡ በዚህም ትልቅ ለውጥና መሻሻል ታይቷል፡፡ ነዳጅ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ንግድ ከ13 ቢሊዮን ዶላር ወደ 30 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል፡፡
ከአሜሪካ ጋር የንግድ ልውውጣቸውን ለማስፋት ፍላጎት የላቸው አገራት የሚያሳዩት እንቅስቃሴ ደግሞ ትብብራችንን ወደላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል፡፡ ለአብነት ያህል ባለፈው ሳምንት ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አሜሪካ የተገኙት የጋናው ፕሬዚዳንት ናና አኩፎ-አዶ እርሳቸውና ሕዝባቸው ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን ትብብር በማጠናከር በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድህነት በመላቀቅ የበለፀገች ጋናን ለመገንባት ያላቸውን ፍላጎት ገልጸውልናል፡፡
አፍሪካ አሁንም ገና ያልተነካ እምቅ አቅም ያላት አህጉር ናት፡፡ የአሜሪካ የግሉ ዘርፍ የአፍሪካ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውልና አህጉሪቱ ተጠቃሚ እንድትሆን የማድረግ ፍላጎትና አቅም አለው፡፡ የአሜሪካ የንግድ ተቋማት ያላቸው የቴክኒክ ልምድ የአፍሪካ አገራት ሀብታቸውን ተጠቅመው እንዲበለፅጉ እድል የሚሰጥ ነው፡፡
በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት (USAID) የሚተገበረው (የሚመራው) ፓወር አፍሪካ ፕሮጀክት፣ በአህጉሪቱ የልማት ታሪክ ውስጥ ከተተገበሩ ግዙፍ የግልና የመንግሥት ዘርፍ የጋራ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ ዓላማም እ.አ.አ በ2030 ለ300 ሚሊዮን አፍሪካውያን 30ሺ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ መተግበር ከጀመረ ወዲህ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ለኑሮ አስፈላጊ ነገሮች መካከል አንዱ የሆነውን ኤሌክትሪክ ማግኘት ችለዋል፡፡ የዚሁ ፕሮጀክት ሁለተኛ ምዕራፍም ባለፈው ሳምንት ይፋ ሆኗል፡፡
ወጣት አፍሪካውያን መሪዎችን ለማፍራት ያለመውና በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እና በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት የጋራ ትብብር የሚተገበረው የበርካታ አፍሪካውያን ወጣቶች ስልጠናዎችን ጨምሮ ልዩ ልዩ ድጋፎችን እያገኙበት ነው፡፡
የፕሬዚዳንቱ አስቸኳይ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ መቋቋሚ እቅድ ፋይዳው ከሌሎቹ የዓለም አካባቢዎች ይልቅ በአፍሪካ የጎላ ነው፡፡ ከ15 ዓመታት በፊት መርሃ ግብሩ ሲጀመር ከነበረው ነባራዊ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ስርጭት እጅግ በብዙ የተሻለ ለውጥና መሻሻል ማምጣት ተችሏል፡፡
አፍሪካ በሙስና ምክንያት በየዓመቱ ብዙ ቢሊዮን ዶላሮችን ታጣለች፡፡ አሜሪካ የአፍሪካ የዴሞክራሲ ተቋማትን በማጠናከር በሙስና የሚመዘበርባትን ሀብት ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት ድጋፍ ታደርጋለች፡፡
በአጠቃላይ አፍሪካ የተሻለ መፃኢ እድል እንዳላት አሜሪካ ታምናለች፡፡ በአፍሪካ የልማትና የብልፅግና ጉዞ አጋር ሆነን የመዝለቅ ፍላጎትና እድል አለን፡፡ ሌሎች አገራት በአፍሪካ ልማትና እድገት ላይ ለመሳተፍ የሚያደርጉትን ጥረትና እንቅስቃሴ እናከብራለን፡፡ አሜሪካ የአፍሪካን እድገትና ልማት የምትደግፈው የሁለትዮሽ ትብብርንና ሉዓላዊነትን ባከበረ መልኩ ነው፡፡
የልዕለ ኃያላኗ ቁጥር አንዱ ዲፕሎማት ለአፍሪካ-አሜሪካ የትብብር መስኮች ሰፋ ያለ ጊዜ በሰጡበት ገለፃቸው፣ ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ጠንከር ባሉ ቃላት ኮንነውታል፡፡ ‹‹የቻይና ኢንቨስትመንቶች ለአፍሪካ መሰረተ ልማት መሟላት ትልቅ አቅም ቢፈጥሩም፣ ቻይና የአፍሪካ አገራት ላይ የዕዳ ጫና በማብዛት አገራቱ ዘላቂ እድገት እንዳይኖራቸው እያደረገች ነው›› ብለዋል፡፡
ሬክስ ቲለርሰን ማን ናቸው?
እ.አ.አ መጋቢት 23 ቀን 1952 ቴክሳስ ውስጥ የተወለዱት ሬክስ ዋይኒ ቲለርሰን፣ የቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ምህንድስና ምሩቅ ናቸው፡፡ እ.አ.አ ከ2006 እስከ 2016 ግዙፉን ኤግዞንሞቢል ኩባንያን መርተዋል፡፡ እ.አ.አ ከየካቲት 1 ቀን 2017 ጀምሮ ደግሞ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ የሦስት ልጆች አባት የሆኑት ቲለርሰን፣ የልዕለ ኃያሏ አገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት የፖለቲካ ልምድ እንደሌላቸው ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

አንተነህ ቸሬ

 

Published in ዓለም አቀፍ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።