Items filtered by date: Tuesday, 01 May 2018

በአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ዓመታዊ ውድድር የሆነው የአዲስ አበባ ብስክሌት ክለቦች የዙር ሻምፒዮና ከመጋቢት 9 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ሲሆን በሻምፒዮናው አራተኛ ሳምንት ላይም የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ክለብ ተሳታፊዎች ደምቀው ታይተውበታል።

በሻምፒዮናው ጠንካራ ተፎካካሪዎችን በማሳተፍ የሚታወቀው የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በ 16 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ማውንቴን ብስክሌት የግል ውድድር ላይ በሴትም በወንድም የበላይነቱን ሲያሳይ በወድድሩም ቅድስት ኡመር ፣ትዕግስት ረታና ትዕግስት ወንድምአገኝ ከአንድ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል።
በርቀቱ በተወዳዳሪዎቹ መካከል ከፍተኛ ፉክክር የነበረ ሲሆን፤ በቀጣይ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚደረጉ ሻምፒዮናዎች አዲስ አበባ ውጤታማ ሴት ብስክሌተኞች እንደሚኖሯት ያመለከተ ተብሏል።
በተመሳሳይ ዘውግ የወንዶች ውድድር የተካሄደ ሲሆን፤የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ከአንድ እስከ ሦስት ተከታትለው በመግባት ሌላ ታሪክ የሰሩ ሲሆን፣ አዲሱ መኮንን፣ ኃይለእየሱስ ኬኔ እንዲሁም አሸናፊ ረታ ከአንድ እስከ ሦስት በመግባትና አጓጊ ፉክክር በማድረግ ውድድሩን አጠናቀዋል።ከዓመት በፊት በተካሄደው ሻምፒዮና በወንዶች ማውንቴን ብስክሌት በሁሉም ዙሮች በተደረገ 382 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የሸፈነ ውድድር አካዳሚው በቡድን የአጠቃላይ ዋንጫና የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቱ ይታወሳል።
በዘንድሮው ጥሩ አቋም ያሳየው ክለቡ በሻምፒዮናው ቀሪ ዙርም የበላይነቱን በማስጠበቅ ወድድሩን ያጠናቅቃል የሚል ግምት እየተቸረውም ይገኛል።
አካዳሚው ይዞት የነበረውና የ31 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ኮርስ የቡድንና የግል ውድድር በዕለቱ ተካሂዶ የነበረ ሲሆን፣ በቡድን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ 3 ሰዓት ከ13 ደቂቃ 41 ሰኮንድ ከ33 ማይክሮ ሰከንድ በማስመዝግብ አሸናፊ ሆኗል። አዲስ የተቋቋመውና ለመጀመሪያ ጊዜ በሻምፒዮናው እየተካፈለ የሚገኘው ብርሃንና ሰላም የብስክሌት ክለብ ደግሞ 3 ሰዓት13ደቂቃ40 ሰኮንድ ከ80 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት በሁለተኝነት አጠናቅቋል።
በግል ውድድርም የብርሃንና ሰላሙ ኃይሌ አወል በአንደኝነት ሲያጠናቅቅ፤ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ክለብ እስጢፋኖስ ከበደ ሁለተኛ ፤ ቢኒያም ሰለሞን አሁንም ከብርሃንና ሰላም ሦስተኛ ደረጃን ይዘው ወድድሩን ፈጽመዋል። የዘንድሮ ውድድር ክስተት የሆነው ብርሃንና ሰላም በተለይ በኮርስ ጠንካራ ተወዳዳሪዎችን ይዞ በመቅረብ አድናቆትን የተቸረው ሆኗል።
በ 2009 ዓ.ም ተካሂዶ በነበረው ሻምፒዮና በወንዶች ኮርስ ውድድር 685 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር በ12ቱ ሳምንታት የሸፈነ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ድምር ውጤት ኢትዮ ኤሌክትሪክ የወርቅ፣ አካዳሚው ብርና የአፍሪካ ስደተኞች ማህበር የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆናቸው ይታወሳል። በሻምፒዮናው ዳግም ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጠንክሮ ቢቀርብም፤ብርሃንና ሰላም በቀላሉ እጅ እንደማይሰጥ እስካሁን በነበረው ሂደት እያስመሰከረ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮናስ ካሳሁን ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ የውድድሩ አላማ ከሰኔ 15 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዘጋጅነት ለሚካሄደው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ከተማ አስተዳደሩን የሚወክሉ ተወዳዳሪዎችን ለመመልመል ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።
አቶ ዮናስ እንደሚሉት፤በ2009 ዓ.ም በተካሄደው ሻምፒዮና በማውንቴን አንድ የብር ሜዳሊያ ብቻ ነበር የተገኘው ፤ይሄም የሚያሳየው አዲስ አበባ በውጤት ደካማ እንደነበር ነው፤ በመሆኑም በዘንድሮው ሻምፒዮና ጥሩ ውጤት ይጠበቃል።
በሻምፒዮናው የአራት ሳምንታት የውድድር ውጤት በኮርስ ውድድር አጠቃላይ ውጤት ብርሃንና ሰላም በአንደኝነት ፣ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ሁለተኝነት እንዲሁም፤ የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በሦስተኝነት ውድድሩን ይመራሉ።
በግል የማውንቴን ውድድር የጋራድ ተወዳዳሪዎች በሦስቱ ውድድሮች የበላይ ሲሆኑ፤በአራተኛው ሳምንት አካዳሚ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ ውጤቱ ከፍ እንደሚል ታውቋል። ውድድሩ በቀጣዩ እሁድ በተለያዩ ዘርፎች የሚቀጥል ሲሆን፣ 12 ዙር ውድድሮችን በማድረግ እስከ ግንቦት መጀመሪያ የሚጠቃለል ይሆናል ብለዋል።

ዳንኤል ዘነበ

 

Published in ስፖርት

የሳምንቱ መጨረሻ በበርካታ የዓለማችን ከተሞች የማራቶንና የጎዳና ላይ ውድድሮች በብዛት የተካሄዱበት ነበር። ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም በበርካቶቹ ውድድሮች የበላይነትን ይዘው በማጠናቀቅ የሳምንቱን መጨረሻ ቀናት በተለያዩ ጎዳናዎች በወርቅ ማጌጥ ችለዋል። በሳምንቱ መጨረሻ የተካሄዱ ውድድሮች በቁጥር በርካታ ስለሆኑም የተሻለ ደረጃ ያላቸውና ትኩረት የሚሰጣቸውን ብቻ መመልከት የግድ ይላል። 

ከነዚህ ውድድሮች መካከል ትልቅ ደረጃ ያለውና ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው የሃምበርግ ማራቶን ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዚህ ውድድር በተለይም በወንዶች ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ይዘው በማጠናቀቅ በጀርመኗ ከተማ ሃምቡርግ ጎዳና አስደናቂ ብቃት ማሳየት ችለዋል።
አትሌት ሰለሞን ዴክሲሳ በዚህ ውድድር 2:06:34 ሰዓት በማስመዝገብ ቀዳሚ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል። ይህም በውድድሩ ታሪክ ሦስተኛው ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ታዱ አባተ በተቀራረበ ሰዓት 2:06:54 በማጠናቀቅ ሁለተኛ ሲሆን፣ እውቁ አትሌት አየለ አብሽሮ 2:07:19 በሆነ ሰዓት በሦስተኛ ደረጃ ውድድሩን ፈፅሟል። ቀደም ሲል የኦሊምፒክ ቻምፒዮን የነበሩ ጠንካራ የኬንያና የዩጋንዳ አትሌቶች በተሳተፉበት የዘንድሮ ሃምቡርግ ማራቶን እኚህ ሦስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ያሳዩት ድንቅ አቋም የበላይነቱን እንዲወስዱ አድርጓቸዋል። በዚህም ኬንያዊው ሰሎሞን ዬጎ በ2:07:37 ሰዓት አራተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፤ የ2010 ለንደን ኦሊምፒክ የማራቶን ቻምፒዮኑ ስቲፈን ኪፕሮቲች 2:07:57 በሆነ ሰዓት አምስተኛ ደረጃን ይዞ ሊያጠናቅቅ ችሏል።
በዚሁ ውድድር በሴቶች በተደረገው ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ባይቀናቸውም ዜግነታቸውን ለውጠው ለሌሎች አገሮች ከሚሮጡ ትውልደ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድሉ አልወጣም። ለባህሬን የምትሮጠዋ ሽታዬ እሸቴ 2:24:51 በማጠናቀቅ ቀዳሚ መሆን ችላለች። ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ብርቄ ደበሌ 2:25:28 ሰዓት ሁለተኛ በመሆን ስታጠናቅቅ፤ ለባህሬን የምትሮጠዋ ሌላኛዋ ትውልደ ኢትዮጵያዊት አትሌት ሚሚ በለጠ በርቀቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፋ 2:26:06 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ ሆና ማጠናቀቅ ችላለች። ለሰላሳ ሦስተኛ ጊዜ በተካሄደው የሀምቡርግ ማራቶን ሰላሳ አራት ሺ ያህል ተሳታፊዎች ተወዳድረዋል።
በአሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ «ጤናማ ኩላሊት» በሚል የተካሄደው የአስር ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጣፋጭ ድል ያጣጣሙበት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ጎዳና ላይ ውድድሮች መጥታ ውጤታማ መሆን የቻለችው የወጣቶች የዓለም የአምስት ሺ ሜትር ቻምፒዮኗ አትሌት ቡዜ ድሪባ በሴቶች አሸናፊ መሆን ችላለች። ቡዜ ርቀቱን ያጠናቀቀችበት ሰዓትም 32:04፡2 ሆኖ ተመዝግቧል። የዱባይ ማራቶን የሦስት ጊዜ አሸናፊዋ አትሌት አሰለፈች መርጊያ የአገሯን ልጅ ተከትላ 32:06፡3 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ ኬንያዊቷ ሞኒካ ጊጌ 32:15፡4 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ ሆና ፈፅማለች። በዚህ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የመጀመሪ ያዎቹን ሁለት ደረጃዎች ለኬንያውያን አትሌቶች አሳልፈው ቢሰጡም እንዳጠቃላይ በውድድሩ ያስመዘገቡት ውጤት መልካም ነው። በዚህም መሰረት ኬንያውያኑ ሮኔክስ ኪፕሩቶ በ27:08፤ ማቲው ኪሜሊ በ27:19 ሰዓት ተከታትለው ገብተዋል። ኢትዮጵያዊው አትሌት ተሾመ መኮንን በ28:10 ሦስተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ፍቃዱ ግርማ 28:36 በሆነ ሰዓት አራተኛ ሆኖ ፈፅሟል።
በጀርመን ዊዝበርግ አስር ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር ኢትዮጵያውያን በተለይም በሴቶች ቀዳሚውን ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁ ሲሆን፣ ልምድና እውቅና የሌላቸው አትሌቶች የተሳተፉበት በመሆኑ ብዙ ትኩረት አልተሰጠውም። ያም ሆኖ ሜላት ይስሃቅ 32:39 በሆነ ሰዓት የውድድሩ አሸናፊ ስትሆን ሃዊ አለሙ በ 33:29 ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች። ኬንያዊቷ ካሮሊን ቺፕኪሞይ 33:34 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ ሆናለች። በወንዶቹ ውድድር ኬንያውያኑ ኢማኑዔል ኪፕሮኖ 28:17 በሆነ ሰዓት የአገሩን ልጅ ቬዲክ ኪፕኮይችን በ28:18 አስከትሎ በቀዳሚነት ገብቷል። ኢትዮጵያዊው አሸናፊ ሞገስ ደግሞ 28:30 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል።
እንደ አጠቃላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በታላላቅ መድረኮችም ይሁን በግል በሚሮጡ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለይም በሴቶች ውጤታማነታቸው እየጎላ የመጣ ሲሆን፣ ባሳለፍነው ሳምንት በተካሄዱ ከትንሽ እስከ ትልቅ ውድድሮችም የሴት ኢትዮጵያውያን ውጤት የጎላ ነበር። የወንድ አትሌቶችን ውጤት በተመለከተ በተለይም በ2017ና ከዚያ በፊት በነበሩ ጥቂት ዓመታት ኦሊምፒክና የዓለም ቻምፒዮናን ጨምሮ ዝቅተኛ ሊባል የሚችል ቢሆንም በያዝነው 2018 የተሻለ ነገር እየታየ ይገኛል። ያሳለፍነው ሳምንትን ጨምሮ ከዚያ በፊት በነበሩ ሳምንታት በተካሄዱ ውድድሮች የተመዘገቡ ውጤቶችም ይህንን ያሳያሉ።

ቦጋለ አበበ

 

Published in ስፖርት
Tuesday, 01 May 2018 21:04

የተሸከሙትን የማይበሉ

ሰዎች እርስ በእርሳቸው «ጥሩ ሰው!» የሚባባሉት መቼ መቼ ይመስላችኋል? አንዳቸው ለሌላቸው የሆነ ነገር ያደረጉ እንደሆነ ብቻ ነው። ይህን ነገር አምኖ ለመቀበል ብዙ ጊዜ ወስጃለሁ፤ «አንድ ሰው የሆነች ነገር ካጎደለብን ከመቅጽበት መጥፎ ሰው ይባላል፤ እንደውበት ጥሩ ሰው መባልም አንጻራዊ ነው» እያለ የሚነተርከኝ አንድ ወዳጄ ነው ያሳመነኝ።
ቆይቼ ከእርሱ የተሻለና የባሰ ነገሩን ሰባኪ ሆኜ አረፍኩት! የጥሩ ሰውነት መስፈርቱ በአብዛኛው «ለእኔ ምን አደረገልኝ?» የሚለው ነው። ልክ የሻሽወርቅን፤ ጎረቤታችንን እኛ ጎረቤቶቻቸው ጥሩ ሰው እንደምንላቸው ማለት ነው።
እውነት ግን የሻሽወርቅ በጣም ጥሩ ሰው ናቸው፤ ማለቴ ለእኛ። ድግስ ደግሰው መጥራት ነው፣ ብሉልኝ ጠጡልኝ ነው፣ የታመመ መጠየቅ ነው፣ ሰርግ አለ የተባለ እንደሆነ ሲሠሩና ሲያግዙ ማደር ነው። በቃ! በማኅበራዊ ሕይወት እንደ እርሳቸው የተሳካለት የለም። እንደ አገር ራሱ ከእርሳቸው ተሞክሮ መውሰድ ቢቻል ያሰኛል።
ታድያ ጥሩ ሰው ያልኳችሁ ለእኛ በሚያደርጉት ነገር ነው። በአንጻሩ ደግሞ ስማቸው በአንድ ጉዳይ በክፉ ይነሳል፤ ለሚያገለግሏቸው ሠራተኞች ክፉ ናቸው። ለምዶባቸው ይሁን ክፋት ሆኖባቸው ባላውቅም፤ «አህያ የተሸከመችውን አትበላም!» ይላሉ፤ ይሄ አባባል ከጎጂ ልማዳዊ ስነቃሎች ተርታ ያልገባው በማወቅ ተዘንግቶ ይሁን ባለማወቅ ተረስቶ እንጃ። ጎጂ ልማዳዊ ስነቃል የሚባል ነገር ያለም አይመስለኝም፤ አለ እንዴ?
ብቻ ግን የእርሳቸውን ነገር በአገልጋይ ሠራተኞቻቸው ቦታ ሆኜ ሳስበው በእውነትም ድርጊታቸው ክፉ የሚያሰኝ ነው። ለምሳሌ ለድግስ ወጥ ከተሠራ የጣፈጠ ምግብ የወጥ ቤት ባለሙያዎች እንዲበሉ አያደርጉም፤ ለብቻው ሽሮ ወጥ እንዲሠሩ ነው የሚያዝዙት። በእርግጥ ቅባት ከበዛበት የተቀናጣ ምግብ ሽሮ ትልቃለች፤ ቢሆንም ይህን ማድረጋቸው ግን እኛ በደግነት ከምናነሳው ስማቸው ጋር አብሮ አይሄድም።
ያበሳጩኛል፤ «የሰው ፍጹም የለም» ይላል የሰፈር ሰው ደግሞ። ምን አለባቸው!? ከደስታ ወይም ከሀዘን ድግስ ውጪ ሌላ በምን ይገናኛሉ? እኔ ደግሞ ጥሎብኝ ይሄን የእርሳቸውን ነገር ሳስብ በትልልቅ ህንጻ ላይ የሚሠሩ የጉልበት ሠራተኞች ደርሰው ትዝ ይሉኛል። እንደእነርሱ የተሸከመውን የማይበላ አለ እንዴ? ባለሀብቶችና የግንባታው ባለቤቶች አንዳንዴ ለሠራተኛው አስፈላጊ የሆኑ ድንገትም አደጋ ቢደርስ የሚከላከሉበትን ነገር መች ይገዛሉ? ይሰስታሉ ልበል? ያውም ለራሳቸው ነውኮ! ከዛ ብሶ ደግሞ የጉልበት ሠራተኞቻቸውን ክፍያ ሲሰጧቸው በስንት ልመና እና ጭቅጭቅ!
እኛ ሰፈር አንዲት ሴት አለች፤ የጉልበት ሠራተኛ ናት። ትልቁ ልጇ ትምህርት ጨርሶ ሥራ ፈላጊ የሆነላት እናት ናት። በሥራ ማጣቱም ለክፍለ ከተማውና ለወረዳው ሥራ ፈጥሯል እንጂ ሥራ መፍጠር አልሆነለትም፤ የፍጡራን ዓላማ ራሱ ገና ያልተገለጠለት ሰው ሆኖባታል። ምን ታድርገው? በአንድ ጊዜ ሥራ አጥም ሥራ ፈላጊም ልጅ አድርሳ እርሷ ግን አላረፈችም፤ ቢደክማትም አትደክምም፤ ትሠራለች።
ደረሰላት ከተባለ ልጇ በታች ያሉትን ሁለት ልጆቿን የቀን ሥራ እየሠራች ነው ያሳደገችው። የማትሸከመው ድንጋይ፣ የማትወጣው የማትወርደው ደረጃ የለም። ፎቅ ብርቋ የነበረች ሰፈራችንን ያጥለቀለቁ ፎቅ ቤቶችና የንግድ ማዕከላት ሁሉ የእርሷ እጅ አለባቸው፤ በአሁንኛ ቋንቋ አሻራዋ አርፎባቸዋል። እርሷ ግን እዛው ናት፤ ዛሬም የሌላ ባለሀብት ህንጻ ሥራ ላይ ድንጋይ ትሸከማለች።
እነዛን ህንጻዎች በመንገዷ ስታልፍ ስታያቸው ምን እንደሚሰማት አላውቅም። ስሜቷ ምን ይሆን እያልኩኝ ግን አሰላስላለሁ፤ ትኮራለች? ወጣ ገባ የሚሉ የዘነጡ ሰዎችን ስታይ ንድድ ይላታል? እግሯን ወለም ብሏት፣ ትከሻዋን ሸክሙ አዝሎት፣ አቧራው ዓይኗ ውስጥ ገብቶ፣ ድንጋይና ብሎኬቱ እጇን ቦጫጭሮት «ኤጭ!» ያለችባቸውን ቀናት ታስታውስ ይሆን? ወይስ ተማርራ አለማወቋ ይገርማታል? መቼም እነዛ ህንጻዎች በብድርም ይሠሩ ባልታወቀ መንገድ በተሰበሰበ ገንዘብ፤ እነ አያ ባለፎቅ ኪራይ እየሰበሰቡ ተኝተው ማደራቸውን ለማሰብስ ፋታ ታገኝ ይሆን?
ልትኮራባቸው የሚገቡ ብዙ ህንጻ ግንባታዎች ላይ ተሳትፋለች፤ ግን የተሸከመችውን ያህል አልበላችም። ደግሞስ ለምን ትኮራለች? ዋጋዋን ማን አስተውሎ እንድትኮራ ይፈቅድላታል? እኔማ እንዴት እንደምትኖር ሳስብ ሁላ የምንኖርበት አገር የተለያየ ይመስለኛል? እንደው ስለሆድ ብቻ እንኳ ቢታሰብ ጤፍ ስንት ነው? ሽሮ ዱቄትስ? ደግሞ በምን ይጋገራል? ውሃ ከየት ይመጣል? ቤትስ?
ገቢዋን እንዴት እንደምታብቃቃው ሳስብ እፈራለሁ። ቀለብ፣ ልብስ፣ ጤና፣ ውሃ፣ መብራት፣ ኪራይ...እንዴት እንደቻለችው። በእርሷ ገቢ እዚህ አገር መኖር እንደሚቻል መገመት በራሱ ተስፋ ነው። ጉሊት የሚሸጡትን ያቆይልን ማለት ነው። እርሷ ልጆቿ ያሳደገችበት ሁኔታ ሳይ፤ ኑሮ ተወዷል ሲሉኝ መኖር ግን እንዳልከበደ በእርግጠኝነት ለመናገር ደፋር ሆኛለሁ። የመንገድ ላይ ነጋዴዎችንም ቢሆን ክፉ አይንካቸው፤ ከየት መጥቶ ይለበስ፤ ጓዳስ ምን እቃ ይኖረው ነበር? «...ጥፍርን አይነሳም» የሚለው ተረት እዚህ ይሠራል።
በእኛ ቤት በኩል ብዙ ጊዜ ስታልፍ ስለማያት ነው መሰለኝ በቀን ለተወሰኑ ሰከንዶች ኑሮዋን አስባለሁ። እንጂ እኔም እንደ የሻሽወርቅ ለጓደኞቼና ለማውቃቸው እንጂ ጥሩ ሰው ሆኜ አይደለም። ግን ሳያት የሻሽወርቅ ያበሳጩኛል። እርሷን ምንም አላደረጓትምኮ! ቤታቸውም ለሥራ ብላ ሄዳ ከእርሳቸው ጋር ተገናኝታ አታውቅም። ግን እንደው «የተሸከሙትን መብላት የለም!» የሚሉ ባለሀብቶች ተወካይ፤ ያገለገላቸውን ከማክበር ይልቅ ጭራሽ ለሥራው የሚገባውን ዋጋ ለመክፈል እንኳ ከሚሰስቱ ወገን የወጡ ይመስሉኛል።
ይህን ሁሉ ሳነሳ ታድያ ጥሩ ሰው የምንለው ለካ ከራሳችን እይታ አንጻር ብቻ እንደሆነ ማረጋገጤ ላይ እጸናለሁ። ፎቅ ያላቸው ሰዎች የተቸገሩትን ረዱ ሲባል እንሰማለን፤ ህንጻዎቻቸውን ለሠሩላቸው፤ ቤታቸውን በጉልበታቸው ለገነቡላቸው፤ ለተላላኳቸው ግን አይደለም። «የተሸከሙትን ባይበሉ እንኳ በድካም ልፋታቸው ልክ ዋጋቸው ይታሰብ!» እላለሁ፤ ይሄ ጥሩነት አይደለም ግዴታ ነው።
ይህን ስል ጥሩ ሰው፤ አለ አይደለ? ለሰው ቅን አሳቢና መልካም፤ ደግ የሆንኩ ይመስለኛል። ሆኜ እንዳልሆነ ግን አውቃለሁ። ቀኝ ጎኔ፤ «ወገኛ! ጥሩ ሰው አናውቅም እንዴ?» ይለኛል። የእኛን ቤት ሠራተኛ፤ የቤታችንን አገልጋይ ማን ጠየቃት? ሰላም!

ሊዲያ ተስፋዬ

 

Published in መዝናኛ


በርካታ ሰዎች የኩላሊት ህመም ድምፅ አልባ ገዳይ መሆኑን አያውቁም፡፡ ህመሙ ለረጅም ጊዜ ምንም አይነት ምልክት የማያሳይ በመሆኑ አብዛኛዎቹ ሰዎች የኩላሊት ታማሚ መሆናቸውን የሚያውቁት ህመሙ አስጊ ደረጃ ላይ ሲደርስ አልያም ለሌላ ህክምና ሄደው ምርመራ ሲያደርጉ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት የኩላሊት ህመም በኢትዮጵያ አሳሳቢ የጤና ችግር እየሆነ ከመምጣቱ አኳያ ህብረተሰቡ ከኩላሊት ህመም ጋር በተያያዘ በቂ ግንዛቤ ኖሮት ጤንነቱን እንዲጠብቅና ጠቃሚ የጤና ምክሮችን እንዲጨብጥ ለማስቻል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የውስጥ ደዌና የኩላሊት ህክምና ስፔሻሊስት ሃኪምና በሆስፒታሉ የኩላሊት ህክምና ክፍሉ ሃላፊ ከሆኑት ከዶክተር የወንድወሰን ታደሰ ጋር አዲስ ዘመን ቆይታ አድርጓል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኩላሊት ህመም ምንድን ነው? እንዴትስ ይከሰታል?
ዶክተር የወንድወሰን፡- ኩላሊቶች እንደማንኛውም የሰውነት ክፍል እጅግ በጣም ብዙ በሆኑ የተለያዩ የህመም አይነቶች ይጠቃሉ፡፡ ይህ በመሆኑም አንድ የሚባል የኩላሊት ህመም የለም፡፡ ኩላሊቶች ከአፈጣጠር ችግር ጀምሮ በእድሜ ምክንያት እስከሚመጡ ውስብስብ የጤና ችግሮች ድረስ እክል ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ የኩላሊት ህመም በአፈጣጠር ችግር፣በኢንፌክሽን፣ምክንያቱ በማይታወቅ የኩላሊት መቆጣት ሊከሰት ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በዋናነት የስኳር በሽታ፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣የኩላሊት ጠጠር መፈጠር፣በዘር የሚወረሱ በሽታዎች፣እጢዎችና ካንሰርን ጨምሮ የኩላሊት ህመምን ያስከትላሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስንት አይነት የኩላሊት ህመሞች አሉ?
ዶክተር የወንድወሰን፡- ብዙ አይነት የኩላሊት ህመሞች ቢኖሩም፤ የኩላሊት እጢዎችና የሽንት ቧንቧ ጠጠር በጣም የተለመዱ የኩላሊት ህመም አይነቶች ናቸው፡፡ በኩላሊቶችና በሽንት ቧንቧዎች ላይ ጠጠር ተፈጥሮ ጠጠሮቹ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ታማሚው ህመም ይሰማዋል፡፡ ሽንት በሚሸናበት ጊዜም ደም ይታየዋል፡፡ ጠጠሮቹ በህክምና ሲወገዱም የህመም ስሜት ይሰማዋል፡፡ የፊኛና የኩላሊት ኢንፌክሽን ደግሞ በመውለድ እድሜ ባሉ ሴቶች ላይ የሚከሰት ሌላኛው የኩላሊት ህመም ነው፡፡ ኢንፌክሽኖቹ ተደጋጋሚ ቢሆኑም በታማሚው ላይ ዘላቂ ጉዳት የሚያስከትሉ አይደሉም፡፡ የኩላሊት ስራ በድንገት የሚታወክባቸው ሁኔታዎችም አሉ፡፡ ይህም ሙሉ ጤነኛ የነበረ ሰው በሌሎች የጤና ችግሮች ምክንያት የኩላሊት የማጣራት አቅም ሲዳከም ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከፍተኛ ደረጃ የሚባለው የኩላሊት ህመም የትኛው ነው?
ዶክተር የወንድወሰን፡- በአሁኑ ወቅት የህዝብን ትኩረት በከፍተኛ ደረጃ የሳበው ዋነኛ የኩላሊት ችግር ዘላቂ የኩላሊት የማጣራት አቅም መዳከም ነው፡፡ በቂ ዝርዝር ጥናት በአገሪቱ ባይደረግም በአለም ላይ በግምት ከ10 እስከ 11 በመቶ የሚሆነው አዋቂ ሰው የኩላሊት ችግር ይኖርበታል ተብሎ ይገመታል፡፡ ይህም በርካታ ቁጥር ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ ውስጥ አብዛኛው ሰው የመጀመሪያ ደረጃና ገፍቶ ለክፋት የማይዳርግ የኩላሊት ችግር ያለበት ነው፡፡ በጣም ጥቂት የሚባሉት ግን የኩላሊት የማጣራት አቅም መዳከም ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ የስኳር በሽታና ከፍተኛ የደም ግፊት ደግሞ ለዘላቂ የኩላሊት ማጣራት አቅም መዳከም ከሚያጋልጡ መንስኤዎች ውስጥ ዋንኞቹ ናቸው፡፡ የሽንት ቧንቧ በተደጋጋሚ በጠጠር መጠቃትና መዘጋት፣ ምክንያታቸው የማይታወቅ የኩላሊት መቆጣት፣ ከቤተሰብ የሚወረሱ የጤና ችግሮችና ሌሎች ችግሮችም ለተጨማሪ የዘላቂ ኩላሊት የማጣራት አቅም መዳከም ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኩላሊት ህመም ዋና ዋና ምልክቶች ምንድን ናቸው?
ዶክተር የወንድወሰን፡- የኩላሊት ህመም ስቃይ አለው ማለት አይደለም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ የኩላሊት መታወክ ችግር ያለባቸው ሰዎች በመጀመሪያ አካባቢ ምንም አይነት የህመም ምልክት አይታይባቸ ውም፡፡ የኩላሊት መታወክ የመጀመሪያዎቹ ደረጃዎች ሊታወቁ የሚችሉት ህመ ምተኛው በጤና ተቋም በመገኘት የላብራቶሪ ምርመራዎች ሲያደርግ ነው፡፡ የኩላሊት የማጣራት አቅም ሲደክምና መወገድ የሚገባው ቆሻሻ ሳይወገድ ሲቀር ምግብ ማስጠላት፣ ማስመለስ፣ የሰውነት መድከም፣ክብደት መቀነስና የመሳሰሉት ምልክቶች የመጨረሻ ደረጃ የኩላሊት መታወክ ምልክት ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ምልክቶች የሌሎች በሽታዎች ምልክቶችም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የኩላሊት መታወክን በጣም መጥፎ የሚያደርገውም ምልክቶቹ ለኩላሊት ችግር የተለዩ ባለመሆናቸው ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኩላሊት ህመም በየትኞቹ የእድሜ ክልል ባሉ ሰዎች ላይ ይከሰታል?
ዶክተር የወንድወሰን፡- የኩላሊት ህመም በሁሉም የእድሜ ደረጃ ባሉ ሰዎች ላይ ሊከሰት የሚችል ነው፡፡ ከአፈጣጠር ጀምሮ የኩላሊት ችግር መነሻ ሊሆን ስለሚችል ህመሙ እድሜ አይወስነውም፡፡ በልጅነት የእድሜ ክልል የኩላሊት ችግር በጣም የተለመደ አይደለም፡፡ የኩላሊት ችግር በብዛት የሚታየው ስኳር፣ ከፍተኛ የደም ግፊትና ሌሎች ዋና መነሻ ችግሮች በሚታዩበት በአርባዎቹና ሃምሳዎች የእድሜ ክልሎች ውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ ነው፡፡ ዛሬ የጀመረ ስኳርና የደም ብዛት በሽታ በስድስት ወር ወይም በአመቱ ለኩላሊት ህመም መነሻ ሊሆን አይችልም፡፡ እነዚህ የጤና እክሎች የኩላሊት መዳከምን ሊያስከትሉ የሚችሉት ቢያንስ ከአስርና አስራ አምስት አመታት በኋላ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኩላሊት ህመም እንዳይከሰት መፍትሄው ምንድን ነው ?
ዶክተር የወንድወሰን፡- የኩላሊት ህመምን እንደማንኛውም የጤና ችግር ከማከም ይልቅ መከላከሉ የበለጠ ተመራጭ ነው፡፡ ሰዎች ለዘላቂ የኩላሊት መታወክ ችግር ከመጋለጣቸው በፊት በትክክለኛው የእድሜ ገደብ ሲደርሱ ጤና ተቋማት በመሄድ ምርመራ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ የደም ግፊትን፣ የስኳር መጠንን፣ በሰውነት ውስጥ ያለውን የቅባት መጠንና በሽንት ውስጥ ያሉ ችግሮችን መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ይህም በሽታውን በቶሎ አውቆ ለበሽታው ተገቢውን መድሃኒት በመውሰድና በመከታተል የኩላሊት ችግር ፈፅሞ ከመነሻው እንዳይከሰት ማድረግ ያስችላል፡፡ በምርመራ ወቅት ድንገት ሰዎች መጠነኛ የኩላሊት ችግር ቢያጋጥማቸው እንኳን የደም ግፊትንና የስኳር በሽታውን በሚገባ በመቆጣጠር ህመሙ እንዳይባባስና ወደመጨረሻ ደረጃ እንዳይደርስ ማድረግ ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኩላሊት ህመም ከተከሰተ በኋላ ምን አይነት ህክምናዎች ናቸው የሚደረጉት?
ዶክተር የወንድወሰን፡- የኩላሊት ህመም ከተከሰተ በኋላ ያለው ህክምና ውስብስብ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት አፅንኦት እየተሰጠው ያለው ዘላቂ የኩላሊት መታወክ ችግር በመሆኑ ኩላሊቶቹ የማጣራት አቅማቸው ሲዳከም የኩላሊትን ስራ ተክተው የሚሰሩ አርተፊሻል መንገዶችን መጠቀም የግድ ያሰኛል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ገና በማደግ ላይ ባሉ አገራትና ውስብስብ የጤና አገልግሎት በሚገባ ባልተስፋፉበት ውስጥ ህክምናው አስቸጋሪና ለአብዛኛው ታካሚ የማይደርስ ይሆናል፡፡ የኩላሊቶች የማጣራት አቅም ፍፁም ሲዳከም በአርተፊሻል ዘዴ ቆሻሻዎቹን ለማስወገድ ዳያሊሲስ የሚባል የህክምና ዘዴ ስራ ላይ ይውላል፡፡ በጣም የተለመደው የዳያሊሲስ ህክምና አይነትም ደም ከህመምተኛው ወደ አርተፊሻል ኩላሊት ማሽን በመውሰድ ለበርካታ ሰአታት ደሙን በማጣራት ዳግም ወደ ህመምተኛው እንዲመለስ ይደረጋል፡፡ ይህም በስታንዳርዱ መሰረት አንድ ታማሚ በሳምንት ሶስት ቀን ለአራት ሰአታት ደም ለማጣራት የአርተፊሻል ኩላሊት ማሽኑን ይጠቀማል ማለት ነው፡፡ ይህም ሰዎች በኩላሊት መታወክ ምክንያት የሚሰሟቸው የህመም ምልክቶች እንዲቀንሱ፣ጉልበታቸው እንዲጨምርና ወደ ስራ እንዲመለሱም ሊያደርግ ይችላል፡፡
ምንም እንኳን ከዲያሊሲስ የኩላሊት ህክምና የበለጠ ውስብስብ ቢሆንም፤ ሌላውና የተሻለው የህክምና አማራጭ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ነው፡፡ ይህም የሌላ ሰውን ኩላሊት ወደ ታካሚው ሰውነት በቀዶ ህክምና በማዘዋወር ኩላሊቶቹ የታወኩበት ሁኔታ ተሻሽሎ የታካሚው ጤና እንዲመለስ የሚያደርግ ነው፡፡ የኩላሊት ንቅለ ተከላ የተሳካ ሲሆን መቶ በመቶ የኩላሊት ስራን ይተካል፡፡ ይሁን እንጂ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ስራ ከተካሄደ በኋላ በርካታ መድሃኒቶችን መወሰድ ይጠይቃል፡፡ የታማሚው ሰውነት አዲስ የገባውን ኩላሊት እንደ ባእድ አካል አውቆ የመከላከል አቅሙ ኩላሊቱን ሊያጠፋው ስለሚሞክር ይህ እንዳይሆን የመከላከል አቅምን የሚያዳክሙና የየራሳቸው የጎንዮሽ ጉዳት ያላቸው መድሃኒቶች ለታካሚው ይሰጣሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ ኩላሊት የመለገስ ባህል ምን ያህል ዳብሯል?
ዶክተር የወንድወሰን፡- በሰለጠነው አለም ለንቅለ ተከላ የሚውል ኩላሊት የሚገኘው ሊሞቱ ከደረሱ ሰዎች ላይ ነው፡፡ በምእራብ አውሮፓና በሰሜን አሜሪካ 50 በመቶ የሚሆነው የኩላሊት ንቅለ ተከላ ፍላጎት የሚሟላው ለሞት ከተቃረቡ ሰዎች ላይ ሲሆን፣ ቀሪው 50 በመቶ ደግሞ በበጎ ፍቃድ ከሚለግስ ቤተሰብ ነው፡፡ የኩላሊት ንቅለ ተከላ የተጀመረባቸው ገና በማደግ ላይ ያሉ በርካታ አገራት አሉ፡፡ ይሁን እንጂ ለመሞት ከተቃረቡ ሰዎች ላይ ኩላሊት ለመውሰድ የሚያበቃ ውስብስብ ቴክኖሎጂ ስለሌላቸው የኩላሊት ንቅለ ተከላን መቶ በመቶ የሚያሟሉት በህይወት ካለ ሰው ኩላሊት በመውሰድ ነው፡፡ ይህንንም ለማድረግ በቅድሚያ ኩላሊት ለመስጠት ፍቃደኛ የሆነ ሰው ያስፈልጋል፡፡ ፍቃደኛ የሆነው ሰው ኩላሊቱን በፍቅር መስጠት ይኖርበታል፡፡ ኩላሊቱን ሲለግስም በቤተሰብ ተፅእኖ ሳይሆን በፍቅር መሆን አለበት፡፡ በቤተሰቡ ውስጥም ቢሆን የገንዘብ ልውውጥ እንዳይኖር ማጣራት ያስፈልጋል፡፡ ኩላሊት ለጋሹ የቅርብ ቤተሰብ መሆን ይኖርበታል፡፡ ጤናውም በዝርዝር የሚፈተሽ መሆን አለበት፡፡ ባጠቃላይም የኩላሊት ንቅለ ተከላ ስራው አጣዳፊ መሆን የለበትም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ኢኮኖሚያቸው ባልዳበረ አገራት ውስጥ ኩላሊትን በበጎ ፍቃድ መስጠት ለጊዜው ተገቢ አይደለም፡፡ ሰው ኩላሊቱን በገንዘብ ላለመስጠቱ ምንም ዋስትና ስለሌለ የበጎ ፍቃድ ሰጪነት መደገፍ የለበትም፡፡ በኢትዮጵያ በርካታ የቤተሰብ አባላት ባሉበት ሁኔታ በቂ ኩላሊት የመለገስ አቅም በመኖሩ ኩላሊትን የሚለግሰው ቤተሰብ ብቻ መሆን አለበት፡፡ በሰለጠኑ አገራት ኩላሊት በበጎ ፍቃድ ይሰጣል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ሰዎች በሰለጠነው ዓለም በገንዘብ ችግር የተነሳ ኩላሊት ይሰጣሉ ተብሎ ስለማይገመት ነው፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

Published in ማህበራዊ

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ሚያዚያ 1 ቀን 1955 ዓ.ም የተቋቋመ ብቸኛ አገር አቀፍ የሠራተኛ ማህበራት ህብረት ነው፡፡ ኮንፌዴሬሽኑ በዘጠኝ ሴክተሮች የተዋቀሩ በስሩ ዘጠኝ የኢንዱስትሪ ፌዴሬሽኖች አሉት፡፡ በስምንት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶቹ እና ፌዴሬሽኖቹ በሠራተኛው ዘንድ ተደራሽ ሆኖ ሠራተኛውን የማደራጀት እንዲሁም መብትና ጥቅሙን የማስከበር ሥራዎች ያከናውናል፡፡ በየደረጃው ያሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች እና ፌዴሬሽኖች ይህን የሚያከናወኑ ባለሙያዎች አሏቸው፡፡ ኢሠማኮ ሠራተኞችን በማህበር ከማደራጀት ጎን ለጎን አንድነታቸው እንዲጠናከር ያደርጋል፤ተከታታይ ስልጠና በመስጠትም ሠራተኛውን ግንዛቤ ያስጨብጣል፡፡
ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር በተያያዘችው ርብርብ በርካታ ኢንዱስትሪዎች እየተከፈቱ ይገኛሉ፡፤ ኢንዱስት ሪዎቹ ለዜጎች የሥራ እድል ይዘው የመጡ ሲሆን ፣የኢንዱስትሪ ሰላምን በማስፈን የሠራተኛውንም ሆነ የኢንዱስትሪውን ተጠቃ ሚነት ማረጋገጥ ይቻላል፡፤ኢሠማኮም በዚህ ዙሪያ እንደሚሰራ ይገልጻል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ129ኛ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ43ኛ ጊዜ‹‹የተረጋጋ የኢንዱስትሪ ሠላም በተደራጀ ሠራተኛ ይረጋገጣል›› በሚል መርህ ዛሬ የሚከበረውን የዓለም ሠራተኞች ቀን ምክንያት በማድረግ ለኢሠማኮ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ጥያቄዎችን አቅርበንላቸው እንደሚከተለው ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡
አዲስዘመን፡- አንዳንድ አሰሪዎች ሠራተኞቻቸው እንዲደራጁ አይፈቅዱምና እናንተ እዚህ ላይ ሠራተኛው እንዲደራጅ ከማገዝ አኳያ ምን እየሰራችሁ ነው?
አቶ ካሳሁን፡- በጣም ጥቂት በሆኑ በአገር ውስጥ ባለሀብቶች ፋብሪካዎችና በአብዛኛው ደግሞ ከውጭ በመጡ ኩባንያዎች ውስጥ የሠራተኛው የመደራጀት መብት አይከበርም፡፡ በዚህም ምክንያት ኮንፌዴሬሽኑ ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ሠራተኛውን ለማደራጀት አገር አቀፍ ዘመቻ አድርጎ ነበር፡፡ ዘጠኙንም የኢንዱ ስትሪ ፌዴሬሽኖችን በማቀላቀል ከኢሰማኮም በማካተት በአገር አቀፍ ደረጃ ባደረግነው በዚህ ዘመቻ ሠራተኛውን በማህበር ለማደራጀት ጥረት አድርገናል፡፡ በዚህም ወደ 264 ማህበራትን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ማደራጀት ችለናል፡፡ ሠራተኛውን ማደራጀት ቢቻልም፣ አሰሪዎች ሠራተኞቹ እንዲደራጁ ፈቃድ አይሰጡም፡፡ ሠራተኛው የመደራጀት መብቱን እንዲጠይቅም አይፈልጉም፡፡
ሠራተኛው ከተደራጀ የደመወዝ ጭማሪ እንዲሁም የተለያዩ የሙያ ደህንነት የሚያስጠብቁ ግብዓትን ይጠይቃል የሚል ስጋት እያደረባቸው ከዚህ ሲሸሹ ይስተዋላል፡፡ እኛ ሠራተኛው እንዲደራጅ በተለያየ ደረጃ ቀደም ሲል እንዳነሳሁልሽ ሙከራ አድርገናል፡፡ በአዲሰ አበባ ብቻ እናደራጃለን ብለን የያዝናቸው ወደ 92 ያህል ድርጅቶች ናቸው፤ እስካሁን ግን እነዚህ ድርጅቶች በእንቢታኝነታቸው እንደጸኑ ናቸው፡፡ እኛ አዋጁን ለሚያስፈጽመው አካል እንሰጣለን እንጂ አሰሪዎችን ማስገደድ አንችልም፡፡
ለምሳሌ በቅርብ ተገንብተው ወደሥራ በገቡ የኢንዱስትሪ ዞኖችና ፓርኮች ላይ ሠራተኛውን ለማደራጀት ጥረት አድርገናል፡፡ ለማደራጀት ጥረት ካደረግንባቸው መካከል ለቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ አንዱ ነው፡፡የፓርኩ አሰሪዎች ግን ፈቃደኞች አይደሉም፡፡ አንድ በኮሪያ ዜጎች የሚተዳደር ሼንትስ የሚባል ኩባንያ ብቻ የመደራጀትን ጥቅም በአግባቡ ጠይቆና ተረድቶ ፈቃደኛ ሆኗል፡፡ይህ ኩባንያ አራት ሺ ያህል ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ ለአራት ሺ ሠራተኛ በፈረቃ ስልጠና ሰጥተን እንዲደራጁ ተደርጓል፡፡
አዲስ ዘመን፡-የውጭ አገር ኩባንያዎች የሠራተኛውን መብት በተመለከተ እየሰሩ ያሉት የአገሪቱን ህግ ተከትለው ነው?
አቶ ካሳሁን፡- እጅግ በጣም ጥቂት የሆኑቱ ህጉን ተከትለው እየሰሩ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ግን የአገሪቱን ህግ ተከትለው እየሰሩ አይደለም፡፡ የሠራተኛው የመደራጀት መብት በሰብዓዊ መብቶች ውስጥ የተካተተ ቢሆንም ፣የአሠሪና ሰራተኛ አዋጁን በአግባቡ ለማክበር ዝግጁ አይደሉም፡፡
አዲስ ዘመን፡-ሠራተኛው የመደራጀት መብቱ እንዲከበርለት የመጠየቁን ያህል ለኢንዱስትሪ ሠላም መጠበቅና ምርታማነት መጨመር የበኩሉን እንዲወጣ ምን ያህል ግንዛቤ ታስይዛላችሁ?
አቶ ካሳሁን፡-እኛ ሠራተኛውን ስናደራጅ መብቱን ብቻ እንዲጠይቅ አይደለም፡፡‹‹የተረጋጋ የኢንዱስትሪ ሠላም በተደራጀ ሠራተኛ ይረጋገጣል›› የሚለውን የዘንድሮውን መሪ ሐሳብ የመረጥንበት ምክንያትም ሠራተኛው መብቱን ከማረጋገጥ ባለፈ የተረጋጋ የኢንዱስትሪ ሠላም እንዲኖር ሰለምንሰራ ነው፡፡ይህ ሲሆን አሰሪውም ሆነ ሰራተኛው ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ መንግሥትም ከባለሀብቱ የሚያገኘው የገቢ ግብር ይጨምራል፡፡ ሦስቱንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ ምርታ ማነት ካላደገ ማንም ተጠቃሚ መሆን እንደማ ይችል እናስተምራለን፡፡ ለሰራተኛው አመራር በዚህ ጉዳይ ስልጠና እንሰጣለን ፡፡ሰራተኞች በተደራጁባቸው ኢንዱስትሪዎች መልካም የሆነ መግባባት ከመኖሩም በተጨማሪ ድርጅቱን እንደ ራስ በመቁጠር በእኔነት ስሜት ስራቸውን የሚሰሩ መሆናቸውን ማየት ችለናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በተለያዩ ኩባንያዎችም ሆነ ድርጅቶች ለሚቀጠሩ ሠራተኞች መነሻ ደመወዝ ያልተቀመጠበት ምክንያት ምን ይሆን?
አቶ ካሳሁን፡-ምክንያታቸው አላስፈላጊ ትርፍ ለማግኘት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት እየተከፈለ የሚገኘው ደመወዝ እንኳን አንድን ቤተሰብ ማስተዳደር ቀርቶ አንድን ሰው ለተወሰነ ቀናት ማኖር አይችልም፡፡መሰረታዊ ፍላጎትን መሸፈን አይደለም የእለት ጉርስን የሚሸፍን ባለመሆኑ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል መቀመጥ አለበት ብለን ዛሬ በምናደርገው ውይይት ላይ በስፋት እናነሳለን፡፡
ይህ ብቻ ሳይሆን እየተሻሻለ ባለው የአሰሪና ሠራተኛ አዋጅም ይህ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል በአዋጁ ውስጥ እንዲቀመጥና በጥናት ተደግፎ መነሻ የደመወዝ ወለል እንዲኖር ጥያቄ አቅርበን እየተዳራደርን እንገኛለን፡፡ ይህን መሰል ጥያቄ እየቀረበልን ያለው ከአስር ዓመት በፊት ጀምሮ ቢሆንም፣ ሊሰማን የወደደ አካል የለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ጥያቄውን ስታቀርቡ ከመንግሥት የሚሰጣችሁ ምላሽ ምንድን ነው?
አቶ ካሳሁን፡-ብዙ ሥራ አጥ ባለበት አገር ዝቅተኛ የደመወዝ መጠን ብንወስን ብዙ ሠራተኛ ሊቀጥሩ አይችሉም ነው የሚባለው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ትክክል አይደለም፡፡ለምሳሌ አነስተኛ ደመወዝ ከሚከፈልባቸው መካከል በዋናት የሚጠቀሱት የውጭ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ መደበኛ ደመወዝ በወር ብር 650 ነው፡፡ ለአብነት በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተጠቀሰው ደመወዝ ነው የሚከፈለው፤ አንዳንዶቹ በዚህ ደመወዝ ላይ የምግብ አበል ብለው ብር 400 ይከፍላሉ፤ ይሁንና የሚደርሳቸው ግን ሙሉ ለሙሉ ሳይሆን ተቀናንሶ ነው፡፡
አሰሪዎቹ በየኢንዱስትሪ ፓርኩ ማህበር አላቸው፡፡ ሠራተኛው ግን የለውም፡፡ ለምሳሌ ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ላይ ወደ 42 ኩባንያዎች አሉ፡፡ በእነዚህ ኩባንያዎች ሁሉ መነሻ ደመወዝ ብር 650 ነው፡፡ከአንዱ ወጥተው ወደ ሌላው ኩባንያ እንዳይገቡ በራሳቸው አሰሪዎቹ የወሰኑት እንጂ ህጉ ይህንን አይልም፡፡
ብር 400 የምግብ አበል ይከፈላቸዋል፤ ይህም ሳይቀናነስ ቢደርሳቸው እንኳ ሊደርሳቸው የሚችለው ብር አንድ ሺ 50 ነው፡፡ አንዳንዶቹን በተለይ ሴቶችን ቀርበን ስንጠይቃቸው በዚህ ደመወዝ ህይወት መግፋት ከባድ ነው፤ ዓረብ አገር ለመሄድ ሁኔታዎች አስኪመቻቹ ድረስ ነው እዚህ የምንቆየው›› የሚል ምላሽ ሰጥተውናል፡ ይህ በሐዋሳ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አበባ አምራች ኩባንያዎች ውስጥ ያሉትም ሠራተኞች ህይወት ተመሳሳይ ነው፡፡
ሌላው በመንግሥት የሚሰጠው ምላሽ ‹‹ይህ ትውልድ ለአገሩ መስዋዕትነት መክፈል አለበት›› የሚል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሠራተኞች አዎ ለአገራቸው መስዋዕትነትን ይከፍላሉ፡፡ ይህ ግን ለአገር አይደለም፡፡ ይህ አመለካከት ሊታረም ይገባል፡፡ አገር ሊጠቅም በሚችለው ነገር ሁሉ እንሳተፋለን፡፡ ለምሳሌ ከሩቁ ምሳሌ ብጠቅስልሽ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ከሠራተኛው ብቻ ብር 16 ሚሊዮን አዋጥተናል፡፡ በቅርቡም ለህዳሴ ግድብ እንዲሁ እናዋጣለን፤ የአገር ጉዳይ ነውና መስዋዕትነትንም እንከፍላለን፡፡
እርግጥን ነው ፤ሥራ አጦችን ኩባንያዎቹ ይቀጥራሉ፡፡ለዚህ አድናቆቱ አለን፤ እናበረታታ ለንም፡፡ ግን ደግሞ ሠራተኛው ተቀጣሪ ነው ይባል እንጂ የሚያገኘው የወር ደመወዝ እልፍ እንዲል ስለማታስችለው ከድህነት ወለል በታች ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ በዚህ አካሄድ ነው አንግዲህ አገሪቱ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ የምትሰ ለፈው?
ቦሌ ለሚ ላይ ሼንቲስ የሚባል ኩባንያ የውጭ ምንዛሬ በጨመረበት ወቅት ለሠራተኞች ብር 200 ሲጨምር በአዲሱም ሆነ በሌላው ኩባንያ ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ በሙሉ ወደዚህ ኩባንያ ለመቀጠር ከፍተኛ ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ ኩባንያው ግን ከመንግሥት ሃላፊዎች ‹‹ከሌሎች ኩባንያዎች ሠራተኞች መውሰድህ ትክክል አይደለም›› በሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል፡፡ እኛ ደግሞ ይህ ስህተት ነው፤ ኩባንያዎቹ በአንድ ገበያ የሚወዳደሩ ናቸውና ሌላው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ታሳርፋለህ፡፡ የሚለው አግባብ አይደለም በሚል እየተናገርን ነው፡፡ ኩባንያው ለሠራተኞቹ ክፍያ ያደረገው እንደሚያዋጣው አውቆ እንጂ በቸርነት ያደረገው አለመሆኑም ሊታወቅ ይገባል ባይ ነኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወደ አገር ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ የሚመጡ ኩባንያዎች አገሪቱ ምቹ የመሰረተ ልማት እንዳላት ሁሉ ርካሽ የሰው ኃይል እንዳላትም ታሳቢ አድርገው ነውና የሚመጡት ይህ ርካሽ የሰው ኃይል ሲባል እንዴት ነው የሚገለጸው?
አቶ ካሳሁን፡- እንደ እኔ አባባሉ በራሱ መልካም አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ብዙ ሊሠራ የሚችል የሰው ሀብት አለ ቢባል የተሻለ ነው፡፡ አባባሉ በራሱ በሠራተኛው አዕምሮ ውስጥ ጥሩ ነገር አይፈጥርም፡፡ ‹‹ርካሽ ነኝ እንዴ›› የሚያስብል ነው፡፡ ለሚመጡት ኩባንያዎች የሚነገረው ‹‹የእኛ አገር ሠራተኛ ብዙ ደመወዝ የሚፈልግ ስላልሆነ በፈለከው የደመወዝ መጠን ልታሰራው ትችላለህ›› ተብሎ ነው፡፡ እንዲያውም ከዛሬ አስር ዓመት በፊት በመንገድ ሥራ ላይ ተሰማርተው ከሚመጡት ውስጥ ‹‹እኛ እኮ ዳቦ ከሰጣችኋቸው ታሰሯችኋላችሁ ተብለን ነው የመጣነው፤ እንዲህ ለመብቱ የሚጠይቅ ሠራተኛ ነው እንዴ ያለው›› ያሉን እንዳሉ አስታው ሳለሁ፡፡
የሠራተኛው መብት ይከበር የሚል ጥያቄ ስናነሳ ደግሞ ‹‹እናንተ ኢንቨስትመንትን ወደኋላ ለማገጓተት ነው›› የሚሉ የመንግሥት ባለስ ልጣናት አጋጥመውናል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ሠራተኛም ሆነ ኢሠማኮ በፍጹም ኢንቨስትመንት እንዲጓተትአይፈልጉም፡፡ምክንያቱም ኢንቨስትመንት ከተጓተተ የሠራተኛው የሥራ ዋስትና በዘላቂነት አይከበርም፡፡ እርግጥ ሥራ አጡ በርካታ የመሆኑን ያህል በርካታ ኩባንያዎች የሉም፤ ሠራተኛው ግን የሚገባውን ሊያገኝ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኩባንያዎች በተቋቋሙበት አካባቢያለውን ማህበረሰብ መጠቀሙ የአካባቢውንም ህብረተሰብ እንደመጥቀም ነውና እዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
አቶ ካሳሁን፡- እንደ ኢሠማኮ ሠራተኛ ድንበር የለውም፤ ኢሠማኮ የትኛውም ቦታና አገር ሄዶ መስራት ይችላል የሚል መርህ አለው፡፡ ነግር ግን አንድን አካባቢ ስናለማ የአካባቢው ማህበረሰብም ተጠቃሚ ቢሆን መልካም ነው፡፡ ፋብሪካው አካባቢው ላይ በመቋቋሙ ምክንያት ኅብረተሰቡን በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት በተፈጠረው አለመረጋጋት በሠራተኛው ላይ ችግር እንዳይፈጠር የተደራጁ ሠራተኞች በተሻለ ሲንቀሳቀሱ ነበር፡፡ ለአብነት የአይካ አዲስ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካን ባነጋገርኩበት ወቅት የሥራ ኃላፊዎቹ እንደነገሩኝ ከሆነ ሠራተኛ ማህበሩ ለፋብሪካው ደህንነት ትልቅ ሚና መጫወቱን ገልጸውልኛል፡፡ እዛው አካባቢ የሚገኝ አንድ ሌላ ፋብሪካ ላይ የተወሰኑ ሠራተኞች ከሌሎች አካላት ጋር ተቀላቅለው በፈጸሙት በጎ ያልሆነ ድርጊት የመንግሥት ባለሰልጣናት ያቺን ስለሰሙ ብቻ ሁሉንም ሠራተኛ ጥፋተኛ አድርጎ የመውሰድ አዝማሚያ ታይቶባቸዋል፡፡ መረጃ ቢጠይቁን ግን ትክክለኛውን መረጃ እንሰጣቸው ነበር፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ሌሎች ፋብሪካዎች አካባቢ የሠራተኛ ማህበራት የሚሰሩበትን ፋብሪካ ሌሊት በባትሪ ሲጠብቁ አድረዋል፡፡ ለአብነት ያህል ማንሳት ካስፈለገ በግርግሩ ወቅት ባህርዳር አካባቢ ጎን ለጎን ያሉ ሁለት የአበባ ማምረቻ ድርጅቶች አሉ፤ ሠራተኛ ማህበር ያለበት ሳይቃጠል፣ የሌለበት ግን ተቃጥሏል፡፡ ሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎችም ተመሳሳይ ሁኔታ ታይቷል፡፡ከሠራተኛ ማህበራቱ አመራር ጋር በስልክ እየተነጋገርን ችግር እንዳይፈጠር ትልቅ ተጋድሎ አድርገናል፡፡
ሠራተኛው ያልተመለሱለት በርካታ ጥያቄዎች እያሉት፣ መሠረታዊ መብቱን ሊጎዳ የሚችል ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ባለበት ወቅት ነበር በአገሪቱ ሁከት የተነሳው፡፡ ይሁንና በዚህ ወቅት ከሠራተኛው ጋር ሰርተን ምንም አይነት ችግር እንዳይፈጠር ማድረግ ችለናል፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በወቅቱ ወዲያው ጥሪያችንን ሰምተው ምላሽ በመስጠ ታቸው ልናመሰግናቸው እንወዳለን፡፡ እርሳቸው በወቅቱ ለመወያየት የሚያስችል ቀና ምላሽ ባይሰጡን ኖሮ እኛ ልንወስድ ያሰብነው የከፋ እርምጃ ነበር፡፡ በመሆኑም በማህበር የተደራጀው ሠራተኛ ይህ ሁሉ ችግር ኖሮበት ከአጥፊው ጋር ተቀላቅሎ ያደረገው ነገር የለም፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን በወቅቱ ስናነሳው በነበረው ጥያቄ ላይ ምላሽ ባይሰጥም ውይይት እየተደረገበት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ምን ያህል ሠራተኛ ተደራጅቷል? ምን ያህልስ ተጠቃሚ ሆኗል ተብሎ ይታሰባል?
አቶ ካሳሁን፡-ወደ 550 ሺ ሠራተኞች ተደራጅቷል፡፡ ይህ ማለት በአንድ ሺ 674 ኩባያዎች ውስጥ ማለት ነው፡፡ ይህ መረጃ እስካለፈው ሰኔ ወር 2009 ዓ.ም ያለውን እንጂ የዘንድሮውን አያካትትም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሠራተኛው ዘንድ አንገብጋቢ ቅሬታ ሆኖ እስካሁን ሲቀርብ የነበረና ምላሽ ያልተሰጠው ጉዳይ ይኖር ይሆን?
አቶ ካሳሁን፡-የመጀመሪያውና ዋነኛ ነው ብለን የምንለው አሁንም በጥያቄ የያዝነውና በረቂቅ ደረጃ ያለው የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ጉዳይ የሠራተኛው ቁልፍ ጥያቄ ነው፡፡ አዋጁ መሻሻል አለበት የሚል ወሳኝ ጥያቄ አለን፡፡
ለአብነት አንድ ጉዳይ ልጥቀስልሽ ‹‹ያለበቂ ምክንያት በወር ሁለት ቀን ያረፈደ አንድ ሠራተኛ በቀጥታ ከስራ ይባረራል›› ይላል ረቂቅ አዋጁ፡፡ የሠራተኛው ዋና ጥያቄ እዚህ ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ ሠራተኛው ከቤት ወጥቶ መንገድ ላይ በራሱ ችግር ሳይሆን በትራንስፖርትም ሆነ በሌላ ምክንያት ሊያረፍድ ይችላል፤ይህ የአስርም ሆነ የአምስት ደቂቃ ማርፈድ በወር ሁለቴ ሊከሰት ይችል ይሆናል፡፡ ይህን ደግሞ አሠሪው በቂ ምክንያት ነው ብሎ አይወስደውም፡፡
እንዲህ አይነቱ ጉዳይ በቂ ምክንያት መሆን ካልቻለ በቂ የሆኑ ምክንያቶች ይዘርዘሩ ስንል ጥያቄ አንስተን ነበር፡፡ ምላሻቸው የነበረው ‹‹ዘርዝረን መጨረስ አንችልም›› የሚል ነበር፡፡ በቂ ያልሆኑ ምክንያቶችስ የትኞቹ ናቸው ብለን በተቃራኒው ስንጠይቅ ደግሞ ‹‹እነሱንም ዘርዝረን መጨረስ አንችልም፤ እናንተ የስራ ባህል እንዲሻሻል አትፈልጉም›› ሲሉ ነው ምላሽ የሚሰጡን፡፡ እንዲህ ከሆነ ብለን አንድ ያቀረብነው አማራጭ ነበር፤ እንደከዚህ በፊቱ በህብረት ስምምነት ይወሰን፤ ምን ያህል ደቂቃ ያረፈደ ምን አይነት ቅጣት ይቀጣል፤ ምን ያህል ያረፈደ ሰው ነው የሥራ ውሉ የሚቋረጠው የሚለውን ጉዳይ ማህበሩና ድርጅቱ በጋራ የሚነጋገሩበትና የሚወስኑበት ጉዳይ ቢሆንስ ብለን ስንል ‹‹አይሆንም›› የሚል አቋም ነው የተያዘው፡፡ ይህ ደግሞ የሠራተኛውን የሥራ ዋስትና የሚያሳጣ ነው፤ የተረጋጋ የኢንዱስትሪ ሠላምንም አያመጣም፤ በመሆኑም ይህን ጉዳይ ሠራተኛው በምሬት ነው የሚያነሳው፡፡ እንዲህ ሲል ሠራተኛው ስራ ጠልቶ ሳይሆን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ስለሚያስገድደው ነው፡፡
ሌላው የመደራጀት ጉዳይ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ የተደራጀ ሠራተኛ ለልማትም፣ለምርትና ምርታማነት ማደግም ማነሳሳት ይችላል፤ እንደ መልካም አጋጣሚ ሊታይ ይገባል እንጂ መኮነን የለበትም፡፡ አሰሪዎች ይህን ጉዳይ ከግንዛቤ ውስጥ እንዲያስገቡት እንጠይቃለን፡፡ በሌላ በኩል ደጋግሜ የማነሳው ትኩረት እንዲሰጠው የምንሻው ጉዳይ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልም በሠራተኛው ዘንድ ትልቅ ጥያቄ መሆኑ ከግምት ወስጥ ገብቶ መልስ ሊያገኝ ይገባል እንላለን፡፡ በአህጉራችን እንኳ 35 የአፍሪካ አገሮች ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል አላቸው፡፡
ሌላው የሙያ ደህንነትና ጤንነት ጉዳይ ነው በትኩረት ሊታይ ይገባዋል ብለን የምንጠይቀው፡፡ ሠራተኛው እጁ እየተቆረጠ፣ አይኑ እየጠፋ ነው፡፡ እንዲያውም በአንድ ፋብሪካ ውስጥ ያጋጠመን ነገር ሠራተኛ ይቀጠራል፡ እጁ ይቆረጣል፤ ይወጣል፡፡አሁንም ያ ጉዳይ ባለመስተካከሉ ይቀጠራል፤ ይቆረጣል፤ ይወጣል፡፡ ይህ ታድያ እስከ መቼ ነው የሚቀጥለው፡፡ አሁን ሥራ ላይ ባለ አዋጅ መሰረት ጉዳቱን ያደረሰው ኩባንያ ቅጣት የሚጣልበት ብር አንድ ሺ 200 ብቻ ነው፡፡ ይህ ወንጀል ነውና ይስተካከል የሚል መልዕክት ነው ያለኝ፡፡
መደራጀትን መንግሥትም ማክበር ይኖርበታል፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች እየተደራጁ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለችው የዛሬ 55 ዓመት ቢሆንም እስከ ዛሬ አልተደራጁም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ካሳሁን፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አስቴር ኤልያስ

Published in ፖለቲካ
Tuesday, 01 May 2018 20:46

የአምራች ሸማች ትስስር

በሀገሪቱ የግብርና ምርትና ምርታማነት በማሳደግ በኩል ከአርሶ አደሩ በተጓዳኝ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ይጠቀሳሉ፡፤የአርሶ አደሮች የህብረት ስራ ማህበራት ከዚህ አንጻር ማንሳት ይቻላል፡፡ ማህበራቱ የአርሶ አደሩን ምርቶች ለገበያ በማቅረብ ለምርቱ ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ ከማስቻል በተጨማሪ እንደ ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር የመሳሰሉትን የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብም ምርትና ምርታማነቱ እንዲያድግ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ለግብርናው ምርትና ምርታማነት እድገት የሚያስፈልጉትን ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ አቅርቦት ከ98 በመቶ በላይ የሚፈጸመው በህብረት ስራ ማህበራት በኩል መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ማህበራቱ በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ ከከተማ ነዋሪዎች የሸማቾች ማህበራት ጋር ትስስር በመፍጠር ገበያ የማረጋጋት ስራም ያከናወናሉ፡፡ ይሀ የማህበራቱ ሚና የሚገኝበትን ሁኔታ አስመልክቶ የተለያዩ ጥያቄዎችን ከፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኤጀንሲው የግብርና ምርቶችን ከከተሞች የሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት ጋር በማስተሳሰር ለከተማ ነዋሪዎች የማቅረቡ ሰራ ምን ይመስላል?
አቶ ኡስማን፡- ኤጀንሲው የአምራቾች የህብረት ስራ ማህበራት ማለትም የገበሬዎች የህብረት ስራ ማህበራት ከሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት ጋር ቀጥተኛ የገበያ ትስስር በመፍጠር ግንኙነቱን እያጠናከረ ይገኛል፡፡ አምራቹ ከሸማች ጋር ያለምንም ተጨማሪ የእሴት ሰንሰለት በመገናኘት ለምርቱ ፍትሃዊ ዋጋ የሚያገኝበት ሁኔታም ተመቻችቷል፡፡ ሸማቹም ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት የሚችልበትን ስርዓት መገንባት አለበት ብለን እየሰራን ነው፡፡ በዚህም ከትንንሽ ከተሞች እስከ አዲስ አበባ ድረስ ሰፊ ትስስር ተፈጥሮ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ይህ ትስስር ሁሉንም አይነት የግብርና ምርቶች ማለትም የብርዕ፣ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህል እንዲሁም አትክልትንና ፍራፍሬን ያካትታል፡፡
አምራቹን ከሸማቹ ጋር በማስተሳሰር ለምርቱ ፍትሃዊ ገበያ ማግኘት እንዲችል ተደርጓል፤ የዚያኑ ያህልም አምራቹ ለሸማቹ በማቅረብ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸጥ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡ ይህ በቀጣይም ይጠናከራል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለሸማቹ የህብረተሰብ ክፍል የግብርና ምርት ግብይትን በአይነትና በመጠን ለማሳደግ ምን ታስቧል?
አቶ ኡስማን፡- የግብርና ምርቶች አቅርቦት እኛ ካሰብነው በላይ በመጠንም በአይነትም እያደገ ነው፡፡ ለአብነት በየከተሞቹ ጤፍ በዓመት ከ500 ሺ እስከ አንድ ሚሊዮን ኩንታል የሚሸጥበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በጥራጥሬም ሆነ ሌሎች ሰብሎችም ተመሳሳይ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል፡፡
ከመጠን በተጨማሪም የምርቶቹ አቅርቦት በአይነትም በጣም እያደገ ነው፡፡ ጤፍ፣ ሽንኩርት እና ቲማቲም ማቅረብ ከተጀመረ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት እንደ ሙዝና የመሳሰሉትን የፍራፍሬ ምርቶች በብዛት ወደ ማቅረብ ተገብቷል፡፡
ይህ ግን በሁሉም የምርት አይነቶች በቂ አቅርቦት አለ ወደሚል መደምደሚያ የሚያደርስ አይደለም፡፡በአቅራቢም ሆነ በተቀባይ በኩል የአመለካከት ችግሮች የሚስተዋሉበት ሁኔታም አለ፡፡ በዚህ ላይ ቀጣይነት ያለው ተግባር በማከናወን የጋራ መግባባት እየፈጠርን በመሄድ ጉድለቶቹን ለመሙላት እየሰራን እንገኛለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሌሎች ምርቶችን በተጨማሪነት የማቅረቡ ሂደት እንዳለ ገልጸውልኛልና ከሸማቹ ጋር በግብርና ምርት የተጀመረው ትስስር ምን ይመስላል?
አቶ ኡስማን፡- የአገር ውስጥ ምርት ትስስሩ በሰብሎችም፣ በአትክልትም እንዲሁም በፍራፍሬም እያደገ የመጣበት ሁኔታ አለ፡፡ ለአብነት ማንሳት ካስፈለገ በመዲናችን አዲስ አበባ የጋሞ ጎፋ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች አርሶ አደሮች ህብረት ስራ ዩኒየን አዲስ አበባ ከሚገኙ ሸማች ዩኒየኖች ጋር ቀጥተኛ የገበያ ትስስር ፈጥሯል፡፡ በዚህ ትስስርም ለምሳሌ አንድ ኪሎ ሙዝ በመዲናችን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጎፋ መብራት ኃይል የጋራ መኖሪያ አካባቢ በ15 ብር ሲሸጥ ከዚያ ብዙም ሳይርቅ ነጋዴው አንድ ኪሎ ሙዝ በ25 ብር ይሸጣል፡፡ ይህ 15 ብር ቀጥታ አርሶ አደሩ ኪስ የሚገባ ገንዘብ ሲሆን፣ በመካከል ደላላ ባለመኖሩ አምራቹም ሆነ ሸማቹ ተጠቃሚዎች የሚሆኑበት ተፈጥሯል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ገበያ ማረጋጋቱ ላይ የተሻለ ሰርተናል ብላችሁ ታስባላችሁ?
አቶ ኡስማን፡- የህብረት ስራ ማሕበራት ሚና በአሁኑ ወቅት በጣም አድጓል፡፡ አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ብዙ ርቀን ሳንሄድ ያለፈው ፋሲካ ላይ ሰፊ የሆነ ርብርብ በመካሄዱ የዋጋ ጭማሪ እንዳይቀጥል ማድረግ ተችሏል፡፡ ከ2008 ዓ.ም እስካሁን ድረስ ሲታይ የነበረው የዋጋ ጭማሪ ግልጽ ነው፡፡ ለአብነት አንድ ኩንታል ጤፍ በአንዳንድ ከተሞች እስከ ሶስት ሺ ደርሶ በነበረበት ወቅት የአምራች ህብረት ስራ ማህበራት ከሸማቾቹ ጋር በፈጠሩት ትስስር ጤፍ በተለይ ባህር ዳርና ሰቆጣ ላይ ከአንድ ሺ 450 እስከ አንድ ሺ 700 ብር ነበር ሲሸጥ የነበረው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ 2008 ዓ.ም ነሐሴ መጨረሻ አካባቢ በአገሪቱ በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት አንድ ኩንታል እስከ ሶስት ሺ 200 ብር ድረስ መሸጡ ይታወሳል፡፡ ይሁንና ምርቱ ከአምራቹ ወደ ሸማቹ ቀጥታ እንዲገባ ለማድረግ በተፈጠረ ትስስር አንድ ኩንታል ጤፍ ከሁለት ሺ 300 እንዳያልፍ ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህ እንግዲህ ቀውሱ የዋጋ ጭማሪ እንዳያስከትል የህብረት ስራ ማህበራቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ያመለክታል፡፡ ይሁንና አሁንም ቢሆን ቀጣይነት ያለው ስራ ይጠይቃልና የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- አንዳንዶች ለከተማ ሸማቹ የሚቀርበው ምርት ጥራት ላይ ጉድለት ይታይበታል፤ ለነጋዴው የተሻለው ምርት ከተሸጠ በኋላ ውዳቂው ነው ለማህበራቱ የሚሰጠው የሚል ነገር ያነሳሉና እርስዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ኡስማን፡- የህብረት ስራ ማህበር በአገር ደረጃ ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋና መለያ ባህሪዎቹ ሶስት ጉዳዮች ናቸው፡፡ አንደኛው ምንነቱና የመጣበት ሁኔታ የሚታወቅ ምርት ማቅረቡ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ጥራቱ ነው፡፡ ሶስተኛው ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው መሆኑ ነው፡፡ ያነሳሽው የጥራት ጉዳይ ማህበራቱ የአርሶ አደሩን ነው የሚያቀርቡት፡፡ አርሶ አደሮች የህብረት ስራ ማህበራት አባላት ናቸው፡፡ አርሶ አደሮቹ ስልጠና የሚወስዱ በመሆናቸው ምርቱ ጥራት የጎደለው አይደለም፡፡ ነገር ግን ከመቶ ኩንታል ጤፍ ውስጥ አንድ ኩንታል እንከን ቢገኝበት የዚያን ያህል ጎልቶ በመውጣት ‹‹ከነጋዴው መግዛት ይሻል ነበር›› የሚባሉ አስተሳሰቦች በሰፊው ሊንጸባረቁ ይችላሉ፤ ስለዚህ በአመለካት ላይ ቀጣይነት ያለው ተግባር ማከናወን ያስፈልጋል፡፡ ይሁንና የጥራት ጉድለት አለ የሚል መደምደሚያ የለንም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ምርት ተቀብለው ወደ ሸማቹ ለማድረስ የሚያሳርፉበትና የሚያከማቹበት በቂ ቦታ እንደሌላቸው ይገለጻል፡፡ ይህም ማህበራቱ የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እንዳይሰጡ እያረገ ነው ይባላልና በዚህ ላይስ ምን ይላሉ፡፡
አቶ ኡስማን፡- ለማህበራቱ ድጋፍ የሚያደርጉ አመራር በሌለበት ከተማ ላይ ሰፊ ችግር ይስተዋላል፡፡ በቂ ቦታ ከሌለ በአነስተኛ ገንዘብ እየገዙ ለሸማቹ ከማድረስ ባሻገር የማከማቸት እድል አይኖርም፡፡ ከዚህም የተነሳ ለአባላቱ ምርት በብዛትና በአይነት ማቅረብ አለመቻላቸው እንደ ችግር ይታያል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ የሚገኙ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የአመራር አባላት ችግሩን ከግምት ውስጥ በማስገባት ቦታ ሊሰጧቸው ይገባል፡፡ ይሁንና ይህ አፈጻጸም ከከተማ ከተማ ሊለያይ ይችላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- አርሶ አደሩ ምርቱ ከፍተኛ በሚሆንበት ወቅት ዋጋው ወድቆ እንዳይጎዳ እንዲሁም በቀጣዩ ምርታማነት ላይም አሉታዊ ተጽእኖ እንዳያሳርፍ ምን እየሰራችሁ ነው?
አቶ ኡስማን፡- የአርሶ አደሩ ምርት እንዳይወድቅ የህብረት ስራ ማህበራት የማይተካ ሚና እየተጫወቱ ናቸው፡፡ ይህ በመሆኑም የአርሶ አደሩ ሀሳብ ቴክኖሎጂን በማሳደግ ምርትና ምርታማነት መጨመር ላይ እየሆነ የመጣው፡፡
ከአራት ዓመት በፊት ከታህሳስ እስከ የካቲት ባሉት ወራት ከፍተኛ ምርት ወደ ገበያ ሲገባ ዋጋ የሚወሰነው በአምራቹ አልነበረም፡፡ ምርቱን ይሰበስብ የነበረው ደላላ አሊያም ሌላ አካል ነበር፡፡ እናም ዋናው ተጠቃሚ አርሶ አደሩ አሊያም ሸማቹ ህዝብ ሳይሆን በመሃል ላይ ያለ ህገ ወጥ አካል ነበር፡፡ ይህ አካሄድ ተቀይሯል፡፡በታህሳስም ሆነ በሌላ ወር በምርት ዋጋ ላይ እምብዛም ልዩነት አይታይም፡፡ በዚህም በኩል የህብረት ስራ ማህበራት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም በየአካባቢው የሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራት የአባሎቻቸውን ምርት በመሰብሰብ ወደ ገበያ ያስገባሉ፡፡ ገበያው ጤናማ እየሆነ በመምጣቱም አርሶ አደሩ ለምርቱ ፍትሃዊ የገበያ ዋጋ ማግኘት እየቻለ ነው፡፡
እርግጥ ነው ማህበራቱ የሀገሪቱን አርሶ አደሮች ምርት ሁሉ መሰብሰብ አይችሉም፡፡ ነገር ግን በአካባቢው መኖራቸው ብቻ የምርቱ ዋጋ የሚረጋጋበት ሁኔታ እንዲፈጠር እያደረገ ነው፡፡ ማህበራቱ የአርሶ አደሩን ምርት ይገዛሉ ተብሎ ስለሚታሰብም ነጋዴው ከአርሶ አደሩ በከፍተኛ ዋጋ ይገዛል፡፡ በዚህም አምራቹ ክፍል ገበያ አጣለሁ የሚል ስጋት ስለማይኖርበት የማምረት ፍላጎቱ እየጨመረ ሄዷል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ኡስማን፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አስቴር ኤልያስ

Published in ኢኮኖሚ

የኮሪያን ምድር ለሁለት የከፈለው ጦርነት ካበቃ ወዲህ ላለፉት ስድስት አሥርት ዓመታት ይለያዩና እርስ በእርስ ይቃረኑ የነበሩት ሁለቱ ኮሪያዎች የዘመን ርቀት፣ የትውልድ ለውጥ እይታቸውን ቀይሮት ዛሬ ላይ መጠላላታቸውን አቁመዋል።ሁለት አገር ቢሆኑም ህዝባቸውን አንድ ለማድረግ ጠላትነታቸውን ወደ ወዳጅነት ለመቀየር የደቡብ ኮሪያው መሪ ሙን ጃኢ-ኢን እና የሰሜኑ አቻቸው ኪም ጆንግ ኡን በጋራ ተወያይተው ከቀናት በፊት እርቅ ይውረድ ብለዋል። የጦርነት ስጋቶችን ወደ ጎን በመተው ኮሪያ ሰርጥን ሠላማዊ ቀጣና ለማድረግ ተስማምተዋል።
በዚህ ታሪካዊ የሁለቱ አገራት መሪዎች ውይይትም አንዱ ሌላውን በሃይል ጨፍልቆ በማስገበር ሁለት የሆነችውን አገር አንድ አድርጎ ከመግዛት ይልቅ ለልዩነታቸው መጥበብ ሠላማዊ ድርድር መፍትሄ ማምጣት እንደሚችል ለዓለም አሳይተዋል። ኮሚኒስትና ካፒታሊስት ርዕዮተ ዓለም አራማጆቹ አገራት አሁን ወደ ሠላም ተቃር በዋል። በጦርነት ውጥረት ውስጥ የቆየው ምድርም አሁን አንፃራዊ ሠላም ሰፍኖበታል።
ዘላቂነቱ ቢያጠያይቅም አሁን የቀድሞ የፒዮንግዮንግ የውጊያ ዛቻ ቀረርቶ እና ፉከራ እንዲሁም ጠብ አጫሪነት ጋብ ብሏል።ለዓመታት አሜሪካን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የሚያስችሉ የኑክሌር መሣሪያዎችን ሠርቻለሁ በማለትና የተለያዩ የኑክሌር አረር ተሸካሚ ሚሳይሎችን ስትሞክር የቆየችው ፒዮንግያንግ፤ ከቀንደኛ ባላንጣዋ አሜሪካ ጋር ለመነጋገርም ፍላጎት አሳይታለች።
የአሜሪካና የሰሜን ኮሪያ ፍጥጫ‹‹በጠረጴዛዬ ላይ የኑክሌር መተኮሻ ቁልፍ አለ›› እስከመባባል የደረሰ ማስፈራራት የታጀበና ከዛሬ ነገ የኑክሌር ጦርነት ይከፈታል በሚል ስጋት አጭሮ መቆየቱን የሚያስታወሱ አካላት ታዲያ፤ የሰሜን ኮሪያ ያልተጠበቀ የአቋም ለውጥ ብዙ አመራምሯዋል።
ለውጡንም ብዙዎች በግርምትና በአድናቆት የተመለከቱት ሁነት ሆኗል። ከሠላም ማስፈኑ እርምጃ ጀርባ ታዲያ በርካታ አስተያየቶች መሰጠት ጀምረዋል። ሰሜን ኮሪያ «በምን ምክንያት የኑክሌር ትጥቅ እስከ መፍታት ድረስ ሊያደርሳት የሚችል ስምምነት ለማድረግ ተዘጋጀች» የሚል ጥያቄም ከሁሉም የገዘፈ ሆኗል።
ሆኖም ሰሜን ኮሪያን ከተለያዩ የዓለም አገሮች ተለይታ እንድትኖር ያደረጓት ማዕቀቦች፣ ሳትወድ በግድ ወደ ጠረጴዛው እንድትመጣ አድርገዋታል የሚሉ አሉ፡፡ ሰሜን ኮሪያ ለኑክሌር መሣሪያ ምርቶቿ ገቢ ከምታገኝባቸው ምንጮችና ከንግድ አጋሮቿ ጋር የነበራት ግንኙነት እንዲቋረጥ መደረጉና፣ ማንኛውም አገር ከሰሜን ኮሪያ ጋር የንግድ ግንኙነት ካደረገ የማዕቀቡ ፍላፃ እንደሚያገኘው በተባበሩት መንግሥ ታት ድርጅትና በአሜሪካ የተሰጡት ማስጠንቀቂያዎች አገሪቱን እንዳዳከሟት የሚያስረዱ የመገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካ ተንታኞችም በርካታ ሆነዋል።
ጎልቶ ባይታይም በዚህ ሂደት የሰሜን ኮሪያ ዘጠና በመቶ የንግድ ኡደት የምትዘውረው ቻይና የአሜሪካ ጥንስስ የሆነው ማዕቀብ በማስተግበር ረገድ ያበረከተችው ሚና የጎላ እንደነበር የሚያትቱም አልጠፉም።እነዚህ አካላት በተለይም በዚህ ዓመት በሰሜን ኮሪያ ላይ በነዳጅ፣ በምግብና ሌሎችም ግብዓቶች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ጫና ማሳደሯ ወደ ሠላም ፊቷን ለማዞሯ ሁነኛ ምክንያት ሆናለች ሲሉ ተደምጠዋል።
የሆነ ሆኖ በሰሜንና ደቡብ ኮሪያ መካከል የተጀመ ረው የመሪዎች ውይይት እንዲሁም በቀጣይ ወራት እንደሚካሄድ የሚጠበቀው የኪምና የትራምፕ ቀጠሮ ከቀጠናው አልፎ ከዛሬ ነገ የኑከሌር ጦርነት ተነሳ በሚል ሲሳቀቅ ለነበረው የዓለም ህዝብ ሰላም ሁነኛ እርምጃ እየተባለለት ይገኛል።
ለዚህ የሠላም ተግባር ተሳታፊ የሆኑ መሪዎች ለሰው ልጅ ደህንነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦችና ድርጅቶች የሚሰጠው የሠላም ኖቤል ሽልማት እንደሚገባቸው የሚሟገቱም በርካታ ሆነዋል። እነዚህ መሪዎች እንደ የነፃነት ታጋዮቹ የሠላም የርህራሄ ምልክቶቹ ማርቲን ሉተር ኪንግ፤ማዘር ተሬዛ፤ እንዲሁም ኔልሰን ማንዴላ ያሲር አራፋት የሠላም ኖቤል ሽልማት ይገባቸዋል የሚል ሃተታን አስፍረዋል።
ይህን እሳቤ በሚመለከት የዋሽንግተን ኤግዛማይነር ኢቫን ቤሪሂል በተለይ የዴይሊ ቴሌግራፉ ዳንኤል ካትሪ እንዳሰፈሩት ትንታኔም ለዶናርድ ትራምፕም ኪምጆንግ የሚሳኤል ልማት ፕሮግራሙን ለማቆም እንዲስማማ ማድረጋቸው የዓለማችንን ወቅታዊ ዋነኛ ስጋት እንደቀነሱ ሊቆጠርላቸው የሚገባ ነው።ይህም ሰውየው ለዓለም ህዝብ ሠላም ሁነኛ አስተዋጾኦ ማድረጋቸው የሚያመላክት ሲሆን፤ዓለም ዓቀፉ የሠላም ሽልማት አዘጋጅ ኮሚቴ ከዚህ በላይ በቂ ማስረጃ አይኖርም። እንደ ፀሃፊዎቹ እምነትም፤ትራምፕ ዓለማችን ግጭቶች እንዲቆምና ሠላማዊ እንድትሆን ፍላጎት እንዳላቸው የሚጠቁም ተግባር እያከናወኑ ነው።በተለይ ኦባማ ስልጣን በያዙ በዘጠኝ ወራቸው አሳኩት ተብሎ ከተሸለሙት አንፃር የትራምፕ ተግባር ይጎላል።
የዘ ኢንዲፔንደንቱ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ዴቪድ ዩዝቦርንም ዶናልድ ትራምፕ ሁለቱ ኮሪያዎች ወደ ሠላም እንዲመጡ በማድረግ ረገድ በተግባር የሚታይ ውጤት ማምጣታቸውን አትቷል።ሰሜን ኮሪያን ከእብሪተኝነቷ ታላቅ የአቋም ለውጥ እንድታደርግ በማድረግ ረገድ ከማንኛውም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በላይ ውጤታማ መሆናቸውን የሚያትተው ፀሃፊው፤ ምንም እንኳን ከባራክ ኦባማ አንፃር ትራምፐ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነት ባይኖራቸውም ሥራቸው ግን ተወዳጅ መሆኑንና ተግባርና ውጤታቸውም ስልጣኑን ካስረከቧቸው ባራክ ኦባማ የተሻለ መሆኑን አብራርቷል።
የ2009 የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ለኖቤል የሠላም ተሸላሚ ቢሆኑም ለዚህ ትልቅ ሽልማት የሚያበቃ ጉልህ ሥራ አልሰሩም በሚል ተቃውሞ ገጥሟቸው እንደነበር በማስታወስም፤ በኒውክሌር ቀውስ እልባት በመስጠት ለዓለም ሠላም አስተዋጾ በማበረከት ረገድ ትራምፕ ከኦባማ የተሻለ ተግባር መፈፀማቸው አስምሮበታል።
እንደ ፀሃፊው እምነት፤ኦባማ በሰሜን ኮሪያን ከስህተቷ ለማረም ዲፐሎማሲም ሆነ ማዕቀብ ሞክረውታል። ይሁንና የትራምፕን ያህል የኢኮኖሚ ጫናና ሰሜን ኮሪያን አደብ የሚያስይዝ የቃላት ማስፈራሪያ መጠቀም አልቻሉም።።በተለይ ማዕቀቡን በማጠንከር ረገድ ትራምፕ የፈጸሙት ተግባር ውጤቱ በግልፅ የሚታይ ነው።
በተለይ ባሳለፍነው ዓመት በትራምፕ ጠንሳ ሽነትና አርቃቂነት በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አስፈፃሚነት በሰሜን ኮሪያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ የነዳጅ የብረት የግብርና ውጤቶችና በመላ ዓለም የሚገኙ የሰሜን ኮሪያ ዜጎችን ጠራርጎ ማስውጣትን ጨምሯል። ይህም ፒዮንግያንግን በእጀጉ አንኮታኩቷታል። ከፀብ ይልቅ የሠላም መንገድን እንድትከተል አስግድዷ ታል ሲል ጸሃፊው አመልክቷል።
አሜሪካ ነጻነቷን ከተቀዳጀች ጀምሮ አገሪቱን በበላይነት በመምራት 45ኛ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ በሰሜንና ደቡብ ኮሪያ መካከል የተጀመረውን ድርድር ያነሳሳሁት እኔ ነኝ” ለአስተዳደሬ እውቅና ሊሰጠው ይገባል፤አያሌ ጠበብት ሞክረውት ያልተሳካው ድርድር እውን ሆኖ መሪዎቹም ለመወያ የታቸው የእኔ ጥረት ያልገባበት ይመስ ላችኋልን?” ሲሉም ጠይቀዋል። ሰውየው አሸናፊ እንዲሁኑ የሚጠየቁ ቅስቀሳዎችም ከመላው ዓለም መሰማት ጀምረዋል።
ከበዓለ ሲመታቸው ጀምሮ በኮሪያ ልሳነ ምድር ሠላም ለማስፋን አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ማረጋገጣቸ ውን ዋቢ በማድረግ የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ሽልማቱ እንደሚገባቸውም የሚገልጹ አሉ።በፒዮንግቻንግ የተካሄደው የበጋ የኦሎምፒክ ጨዋታን የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ሙን ጃዬ ኢን እንደ መልካም አጋጣሚ የተጠቀሙበት ክስተት መሆኑን ያነሳሉ። ሙን ጃዬ ኢን በአንፃሩ ከዚህ ሁሉ ውጤት እኔ ሳልሆን ትራምፕ እውቅናው ይገባቸዋል ሲሉ ተደምጠዋል።
ታላላቅ የኤሲያ ፖለቲካ ጉዳዮችን በመፃፍ የምትታ ወቀው ቶን ጂዬ ቢቢሲ ላይ እንዳሰፈ ራቸው ሀታታና እንደ ኤሲያ ኒውስ ኔትወርክ ኮዳ ሳራሩዋንግ ፤ከሆነ ግን፤ ሙን ጃዬ ኢንን ጨምሮ እውቅናው ለትራምፕ ይገባዋል የሚሉ እጅጉን ተሳስተዋል። ከትራምፕ ይልቅ የደቡብ ኮሪያው መሪ ሙን ጃዬ ኢንን እውቅናው ይገባቸዋል።
እንደ ፀሃፊዎቹ ገለፃም፤የደቡብ ኮሪያው መሪ የዲፐሎማሲ ተግባር ሁለቱን ባላንጣ አገራት ሰሜን ኮሪያና አሜሪካን ወደ ጠረጴዛ ድርድር ማምጣት ችሏል። ሁለቱን እብሪተኛ መሪዎች ወደ አንድ የውይይት መድረክ ማምጣት ደግሞ እጀጉን ትልቅ ጥረት የሚጠይቅና ስኬቱም ሊደነቅ የሚገባው ነው።እናም ፕሬዚዳንቱ እውቅናው ይገባቸዋል ስትል አስቀምጣለች።
ይህ በእንዲህ እያለ ደቡብ ኮሪያ ለምን ለትራምፕ እውቅና ትሰጣለች የሚል ጥያቄ መነሳቱ እርግጥ ነው።ምንም እንኳን እርሳቸው ለትራምፕ እውቅናው ቢሰጡም፤ ይህንን ማድረጋቸውም ከእኔ በላይ ለሚሉት ትራምፕ ከዚህ በላይ መደለያ አለመኖሩን አስምረው በታል።
ሌሎች በአንፃሩ «የለም ኪም ጆንግ ከፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ወዲህ ግትር አቋማቸውን በመተው በሠላም የአብሮነት ግንኙነት ዲፕሎማሲን መከተል ጀምረዋል፥ እናም ከእብሪትና ከጠብ አጫሪነት ተላቀው ለዓለም ሰላም መስፈን የኒውከሌር መርሐ ግብራቸውን እስከማቆም በመድረሳቸው የሠላም ሽልማቱ ይገባቸዋል ያሉም አለጠፉም። እነዚህ ወገኖች ኪምን የሠላም ኖቬል አሸናፊ ማድረግም ሰውየው በቀጣይ አቋማቸውን እንዳይለውጡ ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረክታል ሲሉ ተደምጠዋል።
የተለያዩ መሰል አስተያያቶችን ያስተናገደው የሰሞኑ የሠላም ጉዞ ግን በሁሉም ዘንድ አድናቆት እየተቸረው ነው። የሁለቱ ኮሪያዎች ሠላምም በቀጣዩ ለታቀደው የኪምና የትራምፕ ውይይት ስኬታማነት በር ከፋች ነው ተብሎለታል።
ይሁንና በሦስቱ አገራት የፖለቲካ ጉዞ ላይ አሁንም ቢሆን በርካታ ጥያቄዎች መነሳታቸውን አላቆሙም። «ሰሜን ኮሪያ ቃልና አቋማን በዚህ ትቀጥላለች ወይንስ ቃሏን ታጥፋለች? ለምንስ መሰል የአቋም ለውጥ ማድረግ አስፈለጋት፤አሜሪካና ደቡብ ኮሪያስ ሰሜን ኮሪያን ለማሳመን ምን መስእዋትነት ከፈሉ? የጋራ ወታደራዊ ልምምዳ ቸውን ለማቆም ይስማሙ ይሆን?« የሚሉትም ከሦስቱ አገራት የፖለቲካ አካሄድ ከብዙ በጥቂት ያልተመለሱ ጥያቄዎች ሆነዋል።

ታምራት ተስፋዬ

Published in ዓለም አቀፍ

ኢትዮጵያ በመዋቅራዊ የሽግግር ሂደት ላይ ትገኛለች፡፡ኢኮኖሚዋን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር እያከናወነች ባለችው ተግባርም ለኢንዱስትሪው ዘርፍ መስፋፋት በትኩረት እየሰራች ናት፡፡ በግሉ ዘርፍ፣ በመንግስት የልማት ድርጅቶች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ መንግስት በሚገነባቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባሮች የሚያመለክቱትም ይህንኑ ነው፡፡ ሀገሪቱ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮችንም ለመገንባት እየተንቀሳቀሰች ያለችበት ሁኔታም ይህንኑ ይጠቁማል፡፡
ሀገሪቱ ኢኮኖሚዋን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር ራእይ ሰንቃ በምታደርገው በዚህ ጉዞ የማኑፋክቸሪንግ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ እንዲሁም በውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ የዘርፉን ምርቶችም በሀገር ውስጥ ምርቶች በመተካት ለዚህ የምታውለውን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት አቅዳለች፡፡
በአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ልማትም እንዲሁ ለዘመናት የግብርና ምርቶችን እንዳሉ ወደ ውጭ የምትልክበትን መንገድ በመቀየር እሴት ጨምራ በማምረት ለውጭም ሆነ ለሀገር ውስጥ ገበያ የምታቀርብበት ሂደት ውስጥ ለመግባት እየሰራች ትገኛለች፡፡
በዚህ የኢንዱስትሪ ልማት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት የሚጠበቀውን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብ በኩልም በትኩረት እየሰራች ነው፡፡ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቱ በሀገሪቱ አለመረጋጋት እያለም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ሲሆን፣ሀገሪቱ የገነባቻቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮችም በውጭ ኩባንያዎች እየተያዙ ይገኛሉ፡፡ ኩባንያዎቹ ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ በመላክ ሀገሪቱ የምትፈልገውን የውጭ ምንዛሬ ማስገኘትም ጀምረዋል፡፡
ኢንዱስትሪዎቹ ሲቋቋሙ መሰረት ያደረጉት ምርቶችን ወደ ውጪ መላክ እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መተካትን ብቻ አይደለም፡፡ ለዜጎች የስራ እድል ማስገኘትም ሌላው አላማቸው ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ኢንዱስትሪዎቹ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ላይ ይገኛሉ፡፡ በቅርብ ጊዜ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ለ50 ሺ ሰራተኞች የስራ እድል ፈጥረዋል፡፡
የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ ለ60 ሺ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል እንዲፈጥር ተደርጎ ነው የተገነባው፡፡ የመቀሌና የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮችም ለ50 ሺ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል፡፤ በሌሎች ፓርኮችም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ታስቦ እየተሰራ ነው፡፡
የስራ እድል ጥያቄ በከፍተኛ ሁኔታ እየተነሳበት በምትገኝ ሀገር ይህን ያህል የስራ እድል የሚያስገኝ ተግባር በኢንዱስትሪው መስክ መከናወኑ እንደ ታላቅ ክንውን ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፤
ስለ ኢንዱስትሪ ሲነሳ በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ውስጥ ባለሀብቱ/ኩባንያው. እና ሰራተኛው ይጠቀሳሉ፡፡ አንዱ ያለ አንዱ አይኖርም፡፡ የእነዚህ በሰላም መንቀሳቀስ ኢንዱስትሪው ወደ ፊት እንዲገሰግስ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ምርታማነት እንዲቀጥል ሰላም ወሳኝ ይሆናል፡፡
በኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ያለው ሰራተኛ ስራ ማግኘቱ ብቻ እንደ ታላቅ ተግባር መቆጠር የለበትም፡፡ ለስራው ተገቢውን ክፍያ ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ከዚህ አንጻር የሀገራችን ሰራተኞች በርካታ ጥያቄዎችን ሲያነሱ ይስተዋላል፡፡ የሚከፈላቸው ደመወዝ የሚያኖር አይደለም፡፡ በዚህ የተነሳም ሰራተኛው ስራውን የተሻለ ስራ መፈለጊያ እያረገው ነው፡፡ ስለሆነም ተረጋግቶ እየሰራ እንዳልሆነና ከፍተኛ የሰራተኛ ፍልሰት በኢንዱስትሪው ዘርፍ ይስተዋላል፡፡
ሀገሪቱ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ከምትጠብቃቸው ቱሩፋቶች የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር አንዱ ነው፡፡ይህ ሽግግር ደግሞ ሊከናወን የሚችለው በሰራተኛው በኩል መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ሰራተኛው ከደመወዝ ዝቅተኛነት ከመደራጀት መብት መከላከል ጋር በተያያዘ ተረጋግቶ በማይሰራበት ሁኔታ ይህን ሽግግር ማረጋገጥ አዳጋች ይሆናል፡፡ ሰራተኛው ለተገቢው ስራው ተገቢውን ክፍያ ባላገኘበት ሁኔታ ደግሞ የኢንዱስትሪ ሰላም ማረጋገጥም አይቻልም፡፡
የመብት ጥያቄዎችን ያነሳል በሚል ስጋት ባለሀብቱ የሰራተኛውን መደራጀት አይፈልገውም፡፡ ይህ ግን የተሳሳተ አካሄድ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ የሰራተኛው መደራጀት ለኢንዱስትሪ ሰላም ፋይዳ እንዳለው መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ሰራተኛው ይህን የመብት ጥያቄውን ለማስመለስ የመደራጀት መብቱ ሊጠበቅለት ይገባል፡፡
የሰራተኛው ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ እንደሚሄድ ይጠበቃል፡፡ የዚህን ሰራተኛ ጥያቄ ሳይመልሱ መቆየት ልማቱ በፍጥነት እንዳይጓዝ ማድረግም ይሆናል፡፡ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ሰራተኛውን በመታደግ ኢንዱስትሪው ጉዞው እንዲሰምር ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
አለም አቀፉ የሰራተኞች ቀን ዛሬ በመላው አለም ይከበራል፡፡ ኢትዮጵያም ቀኑ ለ43ኛ ጊዜ ‹‹የተረጋጋ የኢንዱስትሪ ሰላም በተደራጀ ሰራተኛ ይረጋግጣል›› በሚል መሪ ቃል ታከብራለች፡፡ የበአሉ መሪ ሀሳብ ለኢትዮጵያ ወቅታዊም ተገቢም ነው፡፡ የሰራተኛ ማህበራት የሰራተኛው የደመወዝ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ በበአሉ ላይ የሚመለከታቸውን አካላት ላይ ግፊት ማድረጋችን መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡ ለተገቢው ስራ ተገቢው ክፍያ ሊደረግ ይገባል፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

ሀገራችን ኢኮኖሚዋን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር ራእይ ሰንቃ እየሰራች ትገኛለች፡፡ ይህን መዋቅራዊ ሽግግር እውን ለማድረግ ከመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመን አንስቶ እየተሰራ ቢሆንም ፣በተለይ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የመጀመሪያውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመን አፈጻጸም በመገምገም የታየውን ድክምት ለመለወጥ በሚያስችል መልኩ ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
የኢንዱስትሪ ልማቱ የግብርና ምርቶች እሴት ጨምሮ ለገበያ በማቅረብ ላይ እንዲያተኩር ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ምርቶችን በማምረት ለውጪ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ እንዲሁም ከውጪ የሚገባውን የዘርፉን ምርት ለመቀነስ እንደሚያስችል ታምኖበት እየተሰራ ይገኛል፡፤
በግሉ ዘርፍ እንዲሁም በመንግስት የልማት ድርጅቶች ሲካሔድ የቆየው የኢንዱስትሪ ልማት እንዳለ ሆኖ ልማቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ መንግስት እያካሄደ ባለው የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በተለያዩ ክልሎችና አካባቢዎች እየተገነቡ የሚገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮችም ይህንኑ የመንግስትን የኢንዱስትሪ ልማት ቁርጠኝነት ያመለክታሉ፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማቱ ባለሀብቶች ለኢንቨስትመንት መሬት ወስደው መሰረተ ልማት አሟልተው ወደ ስራ ለመግባት ይወስድባቸው የነበረውን ጊዜ እና ያጋጥማቸው የነበረውን የመልካም አስተዳደር ችግር በሚገባ መፍታት ችሏል፡፡
ይህ መንግስት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለማልማት የወሰደው እርምጃ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የውጭ ባለሀብቶች በስፋት ወደ ሀገሪቱ በመምጣት የማምረቻ መሳሪያዎቻቸውን ብቻ በመትከል ወደ ስራ የሚገቡበትን ሁኔታ የፈጠረ በመሆኑ ወደ ሀገሪቱ የሚመጡ ባለሀብቶች፣እያመረቱ ውደ ውጪ የሚልኩት መጠንና የሚያስገኙት የውጭ ምንዛሬም እየጨመረ መጥቷል፡፡ ይህም የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማቱ በትክክለኛ አቅጣጫ ላይ መሆኑን አመላክቷል፡፡
በሀዋሳና ለሌሎች በሀገሪቱ ለሚገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ምሳሌ የሚሆን ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርክ ተገንብቶ ሙሉ ለሙሉ በባለሀብቶች የተያዘ ከመሆኑም በተጨማሪ ምርቶቹን ወደ ውጪ መላክም ጀምሯል፡፡ በመቀሌና በኮምቦልቻም የተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በአሁኑ ወቅት በባለሀብቶች ተይዘዋል፡፡ በአዳማና በድሬዳዋም ግንባታቸው ሲካሄድ የቆየ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በቅርቡ ተጠናቅቀው እንደሚመረቁ ይጠበቃል፡፡ በጅማና በሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ ግንባታዎች እንደሚካሄዱ ይጠበቃል፡፡
ፓርኮቹ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች እየተያዙ ሲሆን፣መንግስት ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ሁኔታዎችን እያመቻቸ መሆኑም በቀጣይ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ እንደሚያጠናከር ይጠበቃል፡፡
ሀገሪቱ በቀጣይም የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች፡፡ እነዚህ የአርሶ አደሩን ምርት በግብአትነት በመጠቀምና እሴት ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ከውጭ የሚመጡ የምግብ ምርቶችን መተካት እንዲሁም የግብርና ምርቶች እንዳሉ ወደ ውጪ ሲላኩ ሀገሪቱ የምታጣውን ገቢ እሴት በመጨመርና ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ግኝቷን ለማሳደግ ያግዛሉ፡
ሀገሪቱ በኢንዱስትሪ ልማት ላይ ስታተኩር ያላትን ሰፊ የሰው ኃይልም ታሳቢ አድርጋ ነው፡፡ ይህን የሰው ሀይል በኢንዱስትሪው መስክ በማሰማራት ለዜጎች የስራ እድል መፍጠር አንዱ ግቧ ነው፡፡ በግሉ ዘርፍ ፣በመንግስት የልማት ድርጅቶች፣ ቻይና ባቋቋመችው የኢንዱስትሪ ዞን እና በመሳሳሉት በርካታ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል አግኝተዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተገነቡ ወደ ስራ በገቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን ደግሞ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል የሚያገኙበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
ከዚህ አንጻር የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ መሉ ለሙሉ ወደ ስራ ሲገባ ለ60 ዜጎች የሰራ እድል እንደሚፈጥር የሚጠበቅ ሲሆን ፣የኮምቦልቻና የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርኮችም ለ50 ሺ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራሉ፡፡ የአዳማና ድሬዳዋ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ስራ ሲገቡ ሊፈጥሩ የሚችሉትን የስራ እድልም ከዚህ አንጻር የሚታይ ይሆናል፡፡
የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከሀገሩ እየለቀቀ ወይም እየተስፋፋ በሌሎች ሀገሮች የሚከትመው የሰው ጉልበትና ጥሬ እቃ ፍለጋ ነው፡፡ ኢንዱስትሪዎቻቸው ጉልበትን በሰፊው የሚጠቀሙ እንደመሆናቸው ለዚህ የሚሆን ጉልበት በሀገራቸው የሚያገኙበት ሁኔታ አየተሟጠጠ መጥቷል፡፡ ስለዚህ መዳረሻቸውን እንደ አፍሪካ ባሉ ሀገሮች አርገዋል፡፡ መዳረሻ ሀገሮችም ይህን መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ምቹ ሁኔዎችን በመፍጠር ገበያውን እየተሻሙ ይገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያም ከዚህ አንጻር ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥረው ይህ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ርብርብ እያደረገች ትገኛለች፡፡ ከኢንቨስትመንት ባለስልጣን የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በየእለቱ በሚያሰኝ መልኩ በርካታ የውጭ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪው መስክ ለመሰማራት ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ናቸው፡፡ ይህም ለበርካታ ዜጎች የሚፈጥርበት ሁኔት እየሰፋ መምጣቱን ያመለክታል፡፡
ከላይ እንደተጠቀሰው የውጭ ኩባንያዎች ወደ ሀገራችን የመጡት ያለውን የሰው ኃይል ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ እርግጥ ነው በኢንዱስትሪዎች ውስጥ ገብቶ ሊሰራ የሚችል ከፍተኛ መጠን ያለው የሰው ኃይል በሀገራችን ይገኛል፡፡ ይህ የሰው ኃይል ግን ይህን ስራ እንደ ስራ ይዞ እንዲቆይ በቂ ክፍያ ምቹ የስራ ሁኔታ ሊኖር ይገባል፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ለሰራተኞች የሚከፈል ደሞዝ የሚያኖር አይደለም፡፡ አንዳንድ ኩባንያዎች ሁኔታዎችን እያዩ ጭማሪ ለማድረግ ቢሞክሩም ተቃውሞ ገጥሟቸዋል፡፡ የኢንዱስትሪ ስራ ስራ መፈለጊያ እየተደረገ እንደሚገኝም ሰራተኛው ይናገራል፡፡ የደሞዝ ጉዳይ በሰራተኛ ማህበራት በኩልም ዋና ጥያቄ ሆኖ እየተነሳ ነው፡፡
መንግስት ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ውስጥ እንደገባ ሁሉ ለሰራተኛው መብት በተለይም ደሞዝ ጉዳይ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ለባለሀብቱ የመወገን ጉዳይ ይታያል፡፡ እርግጥ ነው በብዙ ድካም የመጣ ባለሀብት እንዳይበረግግ መስራት ያስፈልግ ይሆናል፡፡ ከዚህ በመለስ ደግሞ ለዜጎች መሰረታዊ መብት ተቆርቋሪ በመሆን መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ አሰራር መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡
ዛሬ የሰራተኛው ቁጥር ውስን ሊሆንና ድምጹም ላይሰማ ይችላል፡፡ ሀገሪቱ በተያያዘችው የኢንዱስትሪ ልማት ጉዞ ግን የሰራተኛው ቁጥር በጥቂት አመታት ውስጥ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ያኔ ድምጽም የሚሰማበት ሁኔታ እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል፡፡
ከዚህ አንጻር መንግስት ካሉት የሰራተኛ ማህበራት ጋር በመሆን የሰራተኛውን ደሞዝ መነሻ ለማስተካከል እንዲሁም ሌሎች ጥቅማጥቅሞችን የሚያገኝበትን ሁኔታ ከወዲሁ ማከናወን ይኖርበታል፡፡
የኢንዱስትሪ ልማቱ አንዱን እየሰሩ እንዱን እያቆዩ ሊሆን አይገባም፡፡ ያለሰራተኛው ተሳትፎ ኢንዱስትሪው ከንቱ እንደመሆኑ ለሰራተኛው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት መረባረብ ይገባል፡፤
በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ እየገቡ የሚገኙት በአለም ታዋቂ የሚባሉ ኩባንያዎች ሀገሪቱ በተለይ ከቴክኖሎጂ እና እውቀት ሽግግር አኳያ በትኩረት በመስራት በቀጣይ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ዘርፉን የሚረከቡበትን ሁኔታ የሚያመቻችም ነው፡፡ ይህ ደግሞ አንድም ሰራተኛ ላይ የሚሰራ ተግባር ነው፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት በጨርቃጨርቅና አልባሳት ፋብሪካዎች ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች የነገው ባለኢንዱስትሪዎች ናቸው ፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ሰራተኛውን ማቆየት ሲቻል ነው፡፡
ሰራተኛውን በመጀመሪያ ደረጃ ማቆየት የሚቻለው ለስራው ተገቢውን ክፍያ በመስጠት ነው፡፡ ለሰራተኛው ተገቢውን ክፍያ መፈጸም የኢንዱስትሪ ሰላም ማረጋገጥም ነው፡፡ ከዚያም ስልጠናዎችን እየሰጡ ማሳደግም ሲቻል ነው፡፡ ከሁሉም በፊት ግን ቅድሚያ የሚሰጠው ሊያኖር የሚችል ክፍያ መስጠቱ ነው፡፡
እንደሚታወቀው የውጭ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያና መሰል ሀገሮች የሚተሙት በሀገራቸው ያጡትን የሰው ጉልበት ፍለጋ ነው፡፡ እርግጥ ነው በእነዚህ ሀገሮች ከፍተኛ መጠን ያለው የሰው ኃይል እንዳለ ይታወቃል፡፡ የሰው ኃይሉ ስላለ ግን በፈለጉት ደሞዝ ሰራተኛን መቅጠር ተገቢ አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ ምንም እንኳ የስራ እድል ያለህ ለሚለው ዜጋዋ ይህ መልካም እድል ቢመጣላትም፣ የሰራተኛውን ጥያቄ በሌሎቸ ሀገሮች የሚከፈለውንና በሀገሪቱ ያለውን የኑሮ ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ መልኩ የደመወዝ ወለል የሚወጣበት እንደየሁኔታው እያደገ ሊመጣ የሚችልበትን አግባብ የሚመቻችበትን ሁኔታ መስራት ይኖርባታል፡፡ ሰራተኛው የባለሀብቱ መሰረት እንዲሁም የነገው ባለሀብት ሊሆን ይችላልና የደመወዝ ጉዳይ ለነገ የማይባል ብርቱ የቤት ስራ ሊደረግ ይገባል፡፡፡

ዘካሪያስ 

Published in አጀንዳ

አካባቢው ከአዲስ አበባ ራቅ ያለ ነው፡፡ይሁንና በቦታው ላይ የተገነቡት ብዛት ያላቸው ግዙፍ ፋብሪካዎች ሌላ አዲስ አበባ አስመስለውታል፡፡ ፋብሪካዎቹ በአንድ ሰፊ ግቢ ውስጥ ያሉ ቢሆንም በግቢው ውስጥ አንድም የሰዎች እንቅስቃሴ አይስተዋልም፡፡ሁሉም በሥራ ተጠምደዋል፡፡እነዚህን ግዙፍ ፋብሪካዎች ወደ ውስጥ ዘልቆ ላልተመለከተ በውስጣቸው ምን ዓይነት እንቅስቃሴ እየተደረገ ስለመሆኑ መገመት ይከብዳል፡፡ 

በዚህ የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡የሥራ ዕድሉን ከፈጠሩ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች መካከል ሸንተስ የተሰኘው የደቡብ ኮርያው ግዙፍ የጨርቃጨርቅ ውጤቶች አምራች ድርጅት አንዱ ነው፡፡ በዚህ ድርጅት ውስጥ በርካታ ወጣቶች በረድፍ ሆነው በተለያዩ የጨርቃ ጨርቅ ሥራ ደረጃዎች ላይ አንገታቸውን ደፍተው ይሰራሉ፡፡
ወጣት ሰብለ ቸርነት በፋብሪካው ውስጥ በልብስ ስፌት ግብአት አቅራቢነት ትስራለች፡፡ ወደዚህ ሥራ ከመግባቷ በፊት የመስተንግዶ ሥራ ትሰራ ነበር፡፡ከሁለት ዓመት በፊት ለሥራ አጥ ወጣቶች ፓርኩ ያወጣውን የሥራ ማስታወቂያ በመመልከት ተመዝግባ የመወዳደሪያ መስፈርቱን አሟልታ ነው የተቀጠረችው፡፡  እንዲህ ዓይነት ትላልቅ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሀገሪቷ መገንባታቸው በተለይም ለወጣቱ የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንፃር የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ትልቅ መሆኑን የምትገልፀው ወጣቷ፤ይህ ጥሩ ጅምር ይበልጥ ተጠናክሮ ሊሰራበት ይገባል ትላለች፡፡ ወደሥራው ከመግባቷ በፊት ድርጅቱ ስልጠና እንደሰጣትም ገልፃ፣ከዚያ በኋላ ግን ሌሎች ስልጠናዎችን እንዳልወሰደች ታስረዳለች፡፡
ወጣቷ እንደምትለው፤የደመወዝና ሌሎች የመብት ጥያቄዎች ከሠራተኞች በሚነሱ ጊዜ በኃላፊዎች የሚታዩ ሲሆን፣በዚህ መስተናገድ የማይችሉ ከሆነም በድርጅቱ የሠራተኞች ማህበር ተወካዮች በኩል እንዲስተናገዱ ይደረጋል፡፡
የሠራተኛ ማህበሩ በቅርብ ጊዜ የተቋቋመ ከመሆኑ አኳያ በአሁኑ ወቅት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን የምትጠቁመው ወጣቷ፣ ከሠራተኞች የሚነሱ የጥቅምና የመብት ጥያቄዎች ተሰሚነት ቢኖራቸውም ምላሽ ከመስጠት አንፃር ክፍተት እንዳለና ሊስተካከል እንደሚገባው ጠቁማለች፡፡
አሁን ካለው የኑሮ ሁኔታ አንፃር ለሠራተኛው የሚከፈለው የደመወዝ መጠን አነስተኛ መሆኑን የምትገልፀው ወጣቷ፣ በቀጣይ የደመወዝ መጠኑ ሊስተካከል እንደሚገባም ትጠይቃለች፡፡ሥራው ቴክኖሎጂዎችን በየጊዜው የሚጠይቅ ከመሆኑ አኳያም የተለያዩ ስልጠናዎች ሊሰጡ እንደሚገባም ትናገራለች፡፡
ወጣት ሄለን ምንዳም በተመሳሳይ በዚሁ ፋብሪካ ውስጥ በጥራት ቁጥጥር ሥራ ተቀጥራ መስራት ከጀመረች ሁለት ዓመት ሆኗታል፡፡ በአገሪቷ እየተስፋፉ የመጡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተለይም ሥራ አጥ ለሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንፃር ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱም ጠቅሳ፤ እርሷም ይህን ዕድል በማግኘቷ ተጠቃሚ መሆኗን ትገልፃለች፡፡ ወጣት ሄለን በፋብሪካው በቀየችበት ጊዜ ጥሩ የሥራ ልምድ አግኝታለች፡፡ከምትሰራው የሥራ ብዛት አኳያ የሚከፈላት ደመወዝ ፍፁም የተጣጣመ አለመሆኑንም ታስረዳለች፡፡
በድርጅቱ የሠራተኞች ማህበር አባል እንደሆነች የምትገልፀው ወጣት ሄለን፤ በማህበሩ በኩል የሠራተኛውን ጥቅም ከማስከበር አንፃር የሚታዩ ለውጦች እንደሌሉም ነው የምትጠቁመው፡፡ ካለው የኑሮ ውድነት አንፃር ለሠራተኞች የሚከፈለው የደመወዝ መጠን አነስተኛ በመሆኑ ሊሻሻል ይገባል ስትልም ትገልፃለች፡፡ የሥራ ጫና ከመኖሩ አኳያም በተለይ ለሴቶች መስተካከል ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ታመለክታለች፡፡
በሻነተስ የጨርቃጨርቅ አምራች ድርጅት የሰው ሃብትና የጠቅላላ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋእየሱስ ይትባረክ በበኩላቸው እንደሚገልፁት፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በአገሪቱ መስፋፋት በተለይ ለወጣቱ ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ፓርኮቹ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ያላቸውን ወጣቶች በማሳተፍ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡
እንደ ሥራአስኪያጁ ገለፃ ፤የጨርቃጨርቅ ድርጅቱ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከሚገኙት ውስጥ ትልቁ ነው፡፡ ድርጅቱ ባጠቃላይ ከ4ሺ500 በላይ ቋሚ ሠራተኞች በቅጠር እያሰራ ይገኛል፡፡ ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆኑት ሠራተኞች ሴቶች ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ሠራተኞችም ከ18 እስከ 24 ባሉት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ በድርጅቱ በተለያዩ ደረጃዎች ከ100 በላይ የሚሆኑ በዲግሪ ደረጃ የሚሰሩ አሉ፡፡
‹‹በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪው ገና እንጭጭና ያልተለመደ ነው›› የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፣ የፋብሪካ ሥራም በባህሪው ትኩረት የሚሻና ከሠራተኛው በትኩረት መስራትን የሚጠይቅ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በሠራተኛው በኩል ትንሽ ሰርቶ ቶሎ የመልቀቅ አዝማሚያዎች ይታያሉ፡፡ ከኑሮ ውድነቱ አንጻር ለሠራተኛው የሚከፈለው ክፍያም ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ሠራተኞች ሥራቸውን ይለቃሉ ሲሉ ያብራራሉ፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጁ ማብራሪያ፤ የሠራተኛ መልቀቅ እንዳይኖር ለማድረግና ገቢያቸውን ለማሳደግ ድርጅቱ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በፓርኩ ውስጥ መንግሥት በሰጠው ቦታ ላይ 9 ሺ ሠራተኞችን የሚይዝ ባለአስር ፎቅ አስር ብሎክ የማደሪያ ህንፃዎች ግንባታ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ሠራተኛው ለቤት ኪራይ እንዳያወጣ የሚያግዝ ይሆናል፡፡ የአንዱ ብሎክ ግንባታ የተጠናቀቀ ሲሆን በቀጣይ ዓመት የሌሎቹ ህንጻ ግንባታ ይጠቃለላል፡፡
የሠራተኞች ምርታማነትን መነሻ በማድረግ የቦነስ ሥርዓት ውስጥ እንዲገቡም እየተሰራ የሚጠቅሱት ሥራ አስኪያጁ፡፡ ሠራተኛው ወሩን ሙሉ ሳይቀር ቢሰራ ቦነስ የሚያገኝበት ሁኔታ ይመቻቻል፡፡ የተሰጣቸውን ሥራ በብቃት የሚወጡ ሠራተኞችም የቦነስ ተጠቃሚ ይሆናሉ ሲሉ ያብራራሉ፡፡
ሠራተኞች ሙያቸውን እንዲያሳድጉ በድርጅቱ የስልጠና ክፍል እንዲኖር መደረጉን ጠቅሰው፣ ማንኛውም ሠራተኛ በድርጅቱ ሲቀጠር የመጀመሪያ ዙር ስልጠናዎች እንደሚሰጡት፣ ሌሎች ክህሎት የሚጠይቁ ስልጠናዎች ካሉ ሠራተኞቹን ወደ እስያ አገራት በመላክ እንዲሰለጥኑ እንደሚደረግ ያብራራሉ፡፡
ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት፤ በድርጅቱ የሠራተኛ ማህበር አለ፤ማህበሩ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ሲቋቋም የመጀመሪያው ነው፡፡ ከተቋቋመ ገና ሰባት ወሩ ነው፡፡ ሠራተኞች ቅሬታ ሲያጋጥማቸው ለሠራተኛ ማህበሩ ማቅረብ ይችላሉ፡፡ በማህበሩ የሠራተኞች ተወካዮች በመኖራቸውም ችግሮች ቢያጋጥሙ ሠራተኞች የሚሰማቸው አካል እንዳላቸው ይሰማቸዋል፡፡
ማህበሩ ከተቋቋመ በኋላ ምርታማነት ተሻሽሏል የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፣ የማህበሩ መኖሩ ከእያንዳንዱ ሠራተኛ የሚመጣ ቅሬታን ለመቀበልና ለማስተናገድ መርዳቱን ይገልጻሉ፡፡ በመነጋገርና በመደራደር በሠራተኞች መካከል የሚፈጠሩ ችግሮችን መፍታትም ተችሏል ይላሉ፡፡
የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ አስኪያጅ አቶ መንግስቱ ረጋሳ እንደሚገልፁት ፤የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት የሚያያዘው ሀገሪቷ ካስቀመጠችው የልማት ስትራቴጂ አኳያ ነው፡፡ በ2015/17 እ.ኤ.አ አገሪቱ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመመደብና ልማቷን ለማፋጠንና ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር አምራች ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት አለባቸው፡፡ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ይህን ከማስፈፀም አንፃር እንደ ትልቅ መሳሪያ ሆነው ያገለግላሉ፡፡
የሠራተኞችን መብት ከማስጠበቅ አኳያ የውጭ ኢንዱስትሪዎች ወደአገር ውስጥ ሲገቡ በአገሪቱ አሰሪና ሠራተኛ ህግ መሰረት ሥራቸውን እንዲሰሩ ይደረጋል የሚሉት አቶ መንግሥቱ፣ ፓርኩን ሲከራዩም ግንዛቤ እንዲጨብጡ እንደሚደረግም ይናገራሉ፡፡ በተመሳሳይ ለሠራተኞችም እንደ ኢንዱስትሪ ሠራተኝነታቸው መብትና ግዴታዎቻቸውን እንዲያውቁ ይደረጋል ይላሉ፡፡
እንደ አቶ መንግሥቱ ማብራሪያ፤ በአብዛኛው በኢንዱስትሪው የሚሰማሩ ሠራተኞች የኢንዱስትሪ ሥራ ልምዱ እንደሌላቸው ታውቆ፣ራሳቸውን ከኢንዱስትሪው ጋር እንዴት ማዋደድ እንዳለባቸው በቂ ግንዛቤ ይሰጣቸዋል፡፡ ወደ ሥራ ሲገቡ በዓለም ባንክ ድጋፍ ስልጠናዎች ይሰጣቸዋል፡፡
ለወደፊትም በፓርኮች አካባቢ መንግሥት በሚያቀርበው መሬት አማካኝነት ለሠራተኞች የማደሪያ ህንፃዎች እንደሚገነቡ ሥራ አስኪያጁም ጠቁመው፣ይህም ሠራተኛው ተረጋግቶ ሥራውን እንዲሰራ እንደሚያስችል ነው ያብራራት፡፡ 

 ዜና ሀተታ 

አስናቀ ፀጋዬ

 

 

 

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።