Items filtered by date: Thursday, 10 May 2018

በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) በየወሩ የሚወጣ የአገራት እግር ኳስ ወቅታዊ ደረጃ ኢትዮጵያን ባለፈው ወር ከዓለም 145ኛ ላይ አስቀምጧታል፡፡ ከአፍሪካ አህጉር 40 አገሮችን ትከተላለች፡፡ ደረጃው በየትኛውም መመዘኛ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ የስኬት ማጠንጠኛ ሊሆን አይችልም፡፡ ይሁንና እግር ኳሱ ስኬት ርቆት ለዘገባ ባይመጥንም በስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ምክንያት ስሟ ተደጋግሞ ተነስቷል፡፡ የቅርቡ የአዲስ አበባ ስቴዲየም አስደንጋጭ ክስተትም ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃኑ ትኩረት መስፋት ምክንያት ሆኗል፡፡
የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እንግዳ አይደለም፡፡ ነገር ግን ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከመከላከያ ባደረጉት ጨዋታ መጠናቀቂያ የታየው ድርጊት ችግሩ የደረሰበትን ከፍታ የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በወልዲያ ስቴዲየም ያጋጠመው ስፖርታዊ ጨዋነትም በቀጥታ ተላልፎ ብዙዎች ታዝበዋል፡፡ እነዚህ ድርጊቶች በቪዲዮ ምስል በመቅረባቸው ትኩረት አግኝተዋል፡፡ ምስላቸው ባልታዩ በርካታ የክልል ጨዋታዎች የሥነምግባር ችግሮች ቢያጋጥሙም በበዳይና ተበዳይ መካከል ተውጠው ቀርተዋል፡፡ የወልዲያና የአዲስ አበባው ክስተት ግን የታፈኑ በደሎች እንዲሰሙ ምክንያት ሆኗል፡፡ የሰኞውን ክስተት ተከትሎም ዳኞች በማህበራቸው በኩል «ጨዋታ አንዳኝም» ሲሉ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠው ከፌዴሬሽኑ ጋር ለመደራደር ለዛሬ ቀጠሮ ይዘዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ዳኞችና ታዛቢዎች ሙያ ማህበር ያወጣውን ጨዋታዎችን ያለመዳኘት አቋም መግለጫ ተከትሎ ክለቦች በጉዳዩ ላይ ባሳለፍነው ሳምንት መምከራቸው ይታወሳል። የተጎዱ ዳኞች ህክምና ወጪ፣ ኢንሹራንስ፣ ካሳ ክፍያ፣ በስቴዲየሞች የፀጥታ ኃይል ማጠናከር፣ የአውሮፕላን ጉዞ፣ ለተፈፀሙ የመብት ጥሰቶች ሕጋዊ ተጠያቂነት ማረጋገጥ፣ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ማመቻቸት፣ የይግባኝ ኮሚቴዎች አሠራር ግልፅነት እንዲኖረው እንዲሁም ተገቢው የሕግ ከለላ የሚሉት በማህበሩ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ በእነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች የቀጠለው የዳኞቹ ያለማጫወት አድማ ክለቦችንና ፌዴሬሽኑን ስጋት ውስጥ መክተቱ አልቀረም።
የዳኞች ውሳኔና የክለቦች ስጋት
የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ከፌዴሬሽኑ አመራሮች ጋር በነበራቸው ቆይታ ማህበሩ ያስተላለፈውን ውሳኔ እንደሚያከብሩ ደጋግመው ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን እየተንሰራፋ ላለው የስቴዲየም ሥርዓት አልበኝነት መፍትሄ የሚሆነው ጨዋታዎችን ከመዳኘት መቆጠብ እንዳልሆነ ይገልጻሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ክለቦች ከሚያወጡት ከፍተኛ ገንዘብ በተጨማሪ ውድድሩ በሚቋረጥበት ወቅት ከስቴዲየም ትኬት የሚያገኙትን ገቢ ማጣታቸው አሳስቧቸዋል፡፡ የዳኞች ማህበር በበኩሉ አድማውን የጠራው ውድድሩ በመቋረጡ ክለቦች እንዲጎዱ በማሰብ አለመሆኑን ይገልጻል፡፡ ይልቁኑም ይላሉ፤ ፌዴሬሽኑ የችግሩን መጠን ተገንዝቦ ለሕይወታቸው ዋስትና እንዲሰጣቸውና በሥራቸውም እንዲከበሩ ይፈልጋሉ፡፡
የማህበሩ ሰብሳቢ ኢንተርናሽናል ዳኛ ትግል ግዛው፤ ከስቴዲየሙ ክስተት በኋላ ክለቦች ለስፖርታዊ ጨዋነት መስፈን የሰጡትን ትኩረት ያደንቃሉ፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ የክለብ አመራሮች በኩል «የዳኞች ውሳኔ አሰጣጥ የተዛባ መሆን ለሥነምግባር ችግሩ መባባስ አንዱ ምክንያት እየሆነ ነው» በሚል፤ የሚሰነዘርባቸውን ወቀሳ አይቀበሉም፡፡ ወቀሳው በማስረጃ አልተደገፈም ባይ ናቸው፡፡ ክለቦቹ በበኩላቸው፤ ዳኞች ወደተለያዩ ክልሎች ተጉዘው ጨዋታ በሚዳኙበት ወቅት የሚደረግላቸው የተለያየ አቀባበል ለውሳኔዎቻቸው መዛባት ምክንያት እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡
ክለቦቹ ለሕግ ጥሰቱ ግልፅ ማሳያ ባይጠቅሱም ለወቀሳቸው ግን የክልል ጨዋታዎች ቀዳሚ ማጠንጠኛ ናቸው፡፡ ይሄን በተመለከተ «ክለቦች ለዳኞች እጅ መንሻ ይሰጣሉ ይባላል፤ እጅ መንሻውን የሚቀበል ዳኛ ካለ ሰጪዎቹ ክለቦች በመሆናችሁ ተቀባዩን ዳኛ ራሳቸው ያጋልጡ» የሚሉት ኢንተርናሽናል ዳኛ ትግል፤ ለስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ችግሩ ዳኞች ብቻ ተጠያቂ መሆን እንደሌለባቸው ይሞግታሉ፡፡
በስቴዲየሞች ለሚስተዋለው ችግር ጣቶች አሁንም ወደተለያዩ አቅጣጫዎች መቀሰራቸው ቀጥሏል፡፡ ክለቦች ወደ ፌዴሬሽኑ፣ ደጋፊዎች ወደ ዳኞች፣ ዳኞች ወደ ሥነምግባር ኮሚቴ እየወረወሩት ከኃላፊነት መሸሽን የመረጡ ይመስላል፡፡ በዚህም ምክንያት ሲንከባለል ለመጣው ችግር መፍትሄ ከማስቀመጥ ይልቅ ክለቦችን ያሳሰበው የውድድር መቋረጥ ሆኗል፡፡
አሁን ሁሉም ክለቦች የተቋረጠውን ውድድር ለማስቀጠል ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፡፡ ነገር ግን በክለቦቹ መካከል የሚስተዋለው የአቋም የጨዋታ ጊዜ መጀመሩን ከዚህም ሊያርቀው ይችላል፡፡ በአንድ በኩል «ለዳኞች ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ተሰጥቶ ወደ ጨዋታ እንመለስ» የሚሉ ክለቦች ዋናውን የቤት ሥራ ለክለቦች ይሰጣሉ፡፡ በሌላ በኩል «ዳኞች በአቋማቸው ከገፉ ሁለተኛ አማራጭ ማሰብ ተገቢ ነው» በማለት ዳኞችን ከጎረቤት አገሮች የማምጣት ፍላጎት ያንፀባረቁም አሉ፡፡
የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ዳኞችን ከጎረቤት አገሮች ማምጣት ያስፈልጋል የሚለውን አቋም በፕሬዚዳንቱ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ በኩል አስቀምጧል፡፡ ቀሪዎቹ ክለቦች ግን ይሄ ሃሳብ አልተዋጠላቸውም፡፡ እንደብዙዎቹ ክለቦች እምነት የመቶ አለቃ ፈቃደ ሃሳብ በፌዴሬሽኑና ዳኞች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ከመፍታት ይልቅ ችግሩን ወደአላስፈላጊ አቅጣጫ ይወስዳል፡፡ በመሆኑም ውድድሮቹን ለማስቀጠል ሁለተኛ አማራጭ ከማስቀመጥ ይልቅ ፌዴሬሽኑ በአግባቡ ተደራድሮ መፍታት ይገባዋል፡፡
የኮሚቴዎቹ እሰጣገባ
በውይይቱ ወቅት በአብዛኞቹ ክለቦች በኩል ተነስቶ የነበረው ጉዳይ ከሥነምግባር ችግር ማግስት የሚወሰዱ እርምጃዎች ወጥነት የጎድላቸው መሆን ነው፡፡ ክለቦቹ እንደሚሉት፤ ፌዴሬሽኑ የእርምት እርምጃዎችን በመውሰድ በኩል ችግሩ የጎላ ባይሆንም በተለያዩ ወገኖች ጫና የቅጣት ውሳኔዎችን ሲቀለብስ ይስተዋላል፡፡ የተለያዩ ባለሥልጣናት፣ መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም ማህበራዊ ድረገጽ የሚወጡ መረጃዎች ለውሳኔዎች መቀልበስ ምክንያት ናቸው፡፡
የቅርቡን የወልዲያ እግር ኳስ ክለብ ቅጣት ተወያዮቹ በምሳሌነት በማንሳት፤ በሥነምግባር ኮሚቴ ታይቶ ውሳኔ የተሰጠበት ጉዳይ ብዙም ሳይቆይ ውሳኔዎች መቀልበሳቸው በደጋፊዎች ዘንድ አለመተማመን እንዲፈጥር አድርጓል፡፡ የሃዋሳ ከነማ እግር ኳስ ክለብን የወከሉት አቶ ጣሃ አህመድ፤ ከጨዋታዎች በኋላ የሚቀርቡ ሪፖርቶችን ተከትሎ የሚወሰዱ እርምጃዎች ባልታወቁ ምክንያቶች ተደጋግመው ይቀለበሳሉ፡፡ ይሄም የውሳኔዎችን መዘበራረቅ ከማስከተሉ በተጨማሪ ክለቦች በፌዴሬሽኑ አሠራር ላይ እምነት እንዳይኖራቸው አድርጓል፡፡ ለዚህም ፌዴሬሽኑ ያቋቋማቸው ቅሬታ ሰሚና ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴዎች ተናበው አለመስራት ይጠቀሳል፡፡
የፌዴሬሽኑ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተፈራ ደንበል፤ በክለቦች በኩል የሚነሱ ችግሮች ተቀባይነት ያላቸው መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ አያይዘውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሥነምግባር እርምጃዎች በኋላ በተለያዩ መንገዶች የሚስተዋሉ እርምጃውን ከብሔርና ከአላስፈላጊ ጉዳዮች ጋር ማያያዝ መጀመሩን በስጋትነት ይጠቅሳሉ፡፡ ሕጉን መሠረት አድርጎ ቅጣት ለማስተላለፍ የሚቻለው የጨዋታው ኮሚሽነሮች የሚያቀርቡትን ሪፖርት መነሻ በማድረግ ነው፡፡
ሕጎችን መሠረት አድርጎ ውሳኔ ቢተላለፍም በተለያዩ ጫናዎች ምክንያት ቅጣቱ ከቀናት በኋላ ሲቀለበስ የሥነምግባር ኮሚቴው ተጠያቂ ይደረጋል፡፡ ነገር ግን ተጠያቂው ኮሚቴው ሳይሆን የሥራ አስፈፃሚና የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ውሳኔ ነው በማለት ችግሩ ከሥነምግባር ኮሚቴው አቅም በላይ መሆኑን የሚመላክት አስተያየት ይሰጣሉ፡፡ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ገደቡ፤ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች «ፍፁም ናቸው» ባይባልም በተቻለ መጠን በጥንቃቄ እንደሚሰራ በመግለጽ ወቀሳውን ይከላከላሉ፡፡
ክለቦች በማሳያነት ያስቀመጡት የወልዲያ ክለብ ጉዳይም ሕጋዊ አሠራርን መሠረት በማድረግ በሚዛናዊነት የተሰራ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ የሚተላለፉ ቅጣቶችም የአገሪቱ እግር ኳስ ደረጃ ካለበትና ከክለቦች አቅም አንፃር ለማየት እንደሚሞክሩ በመጥቀስ፤ በይግባኝ ሰሚውን ብቃት የሚጠራጠር ካለም ተቀምጦ መፈታተሽ እንደሚቻል ይናገራሉ፡፡ ለአንድ አላማ እየሰሩ በነገሮች ዙሪያ አለመግባባታቸው አግባብ አለመሆኑን የሚጠቅሱት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ መናበብን እንዲያስቀድሙ ያሳስባሉ፡፡
ያልታረሙ ስህተቶች
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ስር ነቀል ለውጥ እስካልመጣ ድረስ ለከፋው የሥነምግባር ጥሰት መፍትሄ አይገኝም የሚለው የብዙዎች እምነት ነው፡፡ ለዚህም ፌዴሬሽኑና ክለቦች በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ በተለያየ ጊዜ ያካሄዱት ውይይት ከመግባባት ሳይደረስ በውይይት ብቻ መቋጨቱ ነው፡፡ የደደቢት እግር ኳስ ክለብን ወክለው የተገኙት ኮሎኔል ዳንኤል፤ በጨዋታ ወቅት ዳኞች የሚሰጧቸውን ውሳኔዎች በመቀበል በኩል ሁሉም ክለቦች ላይ ከፍተኛ ችግር አለ፡፡ ይሄ ስህተት አሁን የተስተዋለ ሳይሆን የመጀመሪያው ዙር የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ሲገመገም በስፋት ተነስቶ ውይይት ተደርጎበት ነበር፡፡ ነገር ግን ወደ ሁለተኛው ዙር የተሻገረው እርማቱ ሳይሆን የገዘፈው ስህተት ሆኗል፡፡
«ሁለተኛው ዙር ከፍተኛ ፉክክር የሚካሄድበት በመሆኑ አሁኑ ይታሰብበት ብለን ነበር» የሚሉት ኮሎኔል ዳንኤል፤ በዚህ ምክንያት አሁን ላይ ክለቦችም ይሁኑ ዳኞች እንዲሁም የጨዋታ ኮሚሽነሮች ወደ ክልል መሄድን ይፈራሉ፡፡ በድፍረት ቢሄዱም የሚሰጡት ውሳኔዎች የተዛቡ እንዲሆኑ ምክንያት ይሆናል፡፡ በመሃል ዳኞች ውስጥ ያለው ስጋት ከመስመር ዳኞች ጋር እንዳይናበቡ እንቅፋት ይሆናል፡፡ መሃል ዳኛ ያፀደቀውን መስመር ዳኛ ይሽራል፤ መስመር ዳኛ ያፀደቀውን ደግሞ መሃል ዳኛ ሲሽረው ይስተዋላል፡፡ እንዲህ ዓይነት የውሳኔዎች መለዋወጥ ደጋፊዎች ላይ የሚፈጥረው ስሜት ወደ ረብሻ ይቀይረዋል፡፡ በቀጣይም ክለቦች በተፅዕኖ ነጥብ ያጣሉ፤ በተፅዕኖ ስቴዲየሞች ሰላም ያጣሉ፡፡ በመጨረሻም «ስፖርት ለልማት» የሚለው «ስፖርት ለስጋት» ወደሚል ይዞራል፡፡
ሃሳቡን የሚያጠናክሩት የኢትዮጵያ ቡና ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ፈቃደ፤ ዳኞችን ማጥቃት የተጀመረው በደጋፊዎች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች እየተባባሱ ከመጡ በኋላ ነው፡፡ ይሄም በሜዳ ላይ ከሚያጋጥሙ አለመግባባቶች በተጨማሪ የፀጥታ ችግር ከተፈጠረ በኋላ የሚወሰዱ እርምጃዎች የተዛቡ በመሆናቸው ነው፡፡ የሌሎች ክለብ አመራሮችም እንደሚሉት የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሩን አስመልክቶ ተደጋጋሚ ውይይት ቢደረግም ምልክቶቹን እንጂ ትክክለኛውን በሽታ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ምክንያቱም የችግሩ ምንጭ ሲሆኑ የሚስተዋሉት የብሔራዊ ሊግ ተወዳዳሪዎች ላይ ገና ብዙ አልተሰራም፡፡
የክለቦች በእኩል አይን አለመታየት፤ የመገናኛ ብዙኃን ሚዛናዊ ያልሆኑ ዘገባዎች፤ ሊጉን የሚያስተዳድር ገለልተኛ አካል አለመኖር፤ የፌዴሬሽኑ የመምራት ብቃት በቂ አለመሆን፤ ክለቦች በውስጣቸው ለሚስተዋለው የሥነምግባር ችግር ተገቢውን ቅጣት አለማስተላለፍ፤ የውሳኔዎች መዘበራረቅ እንዲሁም በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ ተደጋጋሚ መድረኮችን አለማዘጋጀት የሚሉት በውይይቱ ጎልተው የተሰሙ ክፍተቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ስህተቶች ትናንት ሳይታረሙ ያለፉ በመሆናቸው ቀጣይ መፍትሄዎችን ማማተር የግድ ይላል፡፡
መፍትሄ
አሁን በስቴዲየሞች የሚስተዋለው ችግር ሳይውል ሳያድር መፍትሄ ማግኘት የሚገባው ነጥብ መሆኑ ሁሉንም ያግባባል፡፡ ክለቦችም ለዚህ የተለያዩ የመፍትሄ ሃሳቦችን አቅርበዋል፡፡ ሁሉንም ያስማማው ቀዳሚ ነጥብ የመገናኛ ብዙኃን አዘጋገብ ሚዛናዊነት ይኑረው የሚል ነው፡፡ ሆኖም በአንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ዘጋቢዎች በኩል «ሁሉም ክለቦች መገናኛ ብዙኃን ለእከሌ ቡድን ይወግናል ካሉ የሚወገንለት ክለብ ማን ይሆን?» ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ሌላኛው ሁሉንም ያስማማው መፍትሄ የዳኞችን ወቅታዊ ጥያቄ በፍጥነትና በአግባቡ መመለስ ነው፡፡
«መጀመሪያ ክለቦች ወደ ውስጣችን እንመልከት» በማለት የመፍትሄ ሃሳባቸውን የሚጀምሩት የመቀለ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሽፈራው ተክለሃይማኖት፤ ሁሉም ክለብ ተጫዋቾች የሥነምግባር ችግር ሲያሳዩ ተገቢውን ቅጣት መስጠት መጀመር አለባቸው፡፡ የክለባቸው ተጫዋቾች ሜዳ ላይ የዳኛ ልብስ ሲነኩ የደመወዝ ቅጣት እንደሚያስተላልፉም ተሞክሯቸውን ይገልጻሉ፡፡
የአዳማ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ አምበሴ መገርሳ፤ ክለቦች ከክለቦች እርስበእርስ ቅርበት በመፍጠር ስፖርታዊ ጨዋነትን ማረጋገጥ ይችላሉ፡፡ የፌዴሬሽኑ ሚና በአግባቡ መቃኘት አለበት፤ ይግባኝ ሰሚና ሥነምግባር ኮሚቴ ሥራቸው ይናበብ የሚሉም መፍትሄዎች ተጠቁመዋል፡፡ ዘላቂ የስፖርት ፍኖተ ካርታ ይዘጋጅ፤ ክለቦችና አመራሮች ለደጋፊዎች ሥልጠና ይስጡ፤ ለከፍተኛ የሥነምግባር ጥሰቶች በሌሎች ወንጀሎች ላይ የሚተገብራቸው ሕጎችን መውሰድ ይጀምር እንዲሁም የስቴዲየሞች የፀጥታ ሁኔታ ይጠናከር የሚሉት መፍትሄዎች ተቀምጠዋል፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት እስካሁን በተለያዩ ስቴዲየሞች በተፈጠሩ ረብሻ ከአስር በላይ ዳኞች ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር ሰለባ የሆኑት ግን በርካቶች ናቸው፡፡ በአንድ በኩል ደጋፊ ከደጋፊ፤ በሌላ በኩል ደጋፊ ከዳኛ አሁን ደግሞ የቡድን መሪ ተጨምሮበት ችግሩ በአሳሳቢነቱ ቀጥሏል፡፡ ትናንት ዳኞች ቆመው ጥቃት ደርሶባቸዋል፤ አሁን ደግሞ ሮጠውም አልተረፉ፡፡ የክለብ አመራሮቹ የጨዋታዎች መቋረጥ ቢያሳስባቸውም የስፖርቱ ቤተሰቦች ግን «ከጨዋታው ይልቅ ጨዋነቱ ይቅደም» እያሉ ነው፡፡ የተጠቀሱት መፍትሄዎች ደረጃ በደረጃ ካልተወሰዱ የሥነምግባር ጥሰቱ ነገ የሚያስከትለው ቀውስ እጅግ የከበደ ሊሆን ይችላል፡፡

ብሩክ በርሄ

 

ኢትዮጵያ በወጣቶች ኦሊምፒክ ቦክስ ትካፈላለች

 

በሞሮኮ ካዛብላንካ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው የአፍሪካ የወጣቶች ቦክስ ሻምፒዮና በከፍተኛ ፉክክር ታጅቦ እንደቀጠለ ነው። ከዓለም አቀፉ የቦክስ ማህበር ከአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ጋር በትብብር የሚዘጋጀው ሻምፒዮናው ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ተወዳዳሪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ። አምስት የኢትዮጵያ ቦክሰኞች ተሳታፊ በሆኑበት ሻምፒዮና ሁለት የነሐስ ሜዳሊያ ተመዝግቧል። የመጀመሪያው ሜዳሊያ በሴቶች በኩል በብቸኝነት ሀገሯን የወከለችው ቦክሰኛዋ ሃና ደረጀ ተመዝግቧል።
የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ሰልጣኟ ሃና የ48 ኪሎ ግራም ተወዳዳሪ ስትሆን፤ የነሐስ ሜዳሊያ በማግኘት ለፍጻሜ ውድድር አልፋለች። ይህም ከአራት ወራት በኋላ ለሚካሄደው ኦሊምፒክ ማለፏን የሚያረጋግጥላት ሆኗል። ነገ በሚካሄደው ፍጻሜ ከቱኒዚያዊቷ ቦክሰኛ ጋር የምትፋለም ሲሆን፤ አሸናፊ ከሆነች የወርቅ ሜዳሊያ የምታጠልቅ ይሆናል። ሃና ባስመዘገበችው ውጤት ከወራት በኋላ በሚካሄደው የዓለም ወጣቶች ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በቦክስ ስፖርት ተሳታፊ እንድትሆን አስችላለች።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ፍሬ የሆነውና የአዲስ አበባ ፖሊስ ቦክስ ክለብን በ49ኪሎ ግራም የሚወዳደረው እንዳሻው አላዩ የነሐስ ሜዳሊያ ማጥለቁን ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያሳያል። እንዳሻው ነገ ምሽት ከቱኒዚያ አቻው ጋር በሚካሄደው ውድድር የሚያሸንፍ ከሆነም፤ ለፍጻሜው ውድድር ከማለፉም ባሻገር በኦሊምፒኩ ተሳታፊ የሚሆን ሌላው ኢትዮጵያዊው ይሆናል። ዛሬ ምሽት በሚካሄደው 64ኪሎ ግራም የወንዶች ውድድርም ኢትዮጵያዊው ተመስገን ምትኩ ከደቡብ አፍሪካው ቦክሰኛ ጋር የሚገናኝ ይሆናል።
ዓለም አቀፉ የቦክስ ማህበር ከአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ጋር በመሆን በሚዘጋጀው የአፍሪካ የወጣቶች ቦክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ አምስት ቦክሰኞችን በማሳተፍ ላይ እንደምትገኝ ይታወቃል። ቡድኑ በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ የቦክስ አሰልጣኝ ከድር ከማል እየተመራ ነው፤ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ወደ ካዛብላንካ ያቀናው። ሻምፒዮናው እስከመጪው እሁድ የሚቆይ ሲሆን፤ አሸናፊ ቦክሰኞች በወጣቶች ኦሊምፒክ እንዲሁም በአፍሪካ ሻምፒዮና ሀገራቸውን የሚወክሉም ይሆናል።

ብርሃን ፈይሳ

Published in ስፖርት

ከምኑ እንጀምር፡፡ ከስብስባ ታሪካዊ አመጣጥ ወይስ ከ‹‹ዋይፋይ›› ታሪካዊ አመጣጥ? ለነገሩ የሁለቱስ ታሪካዊ አመጣጥ ምን ይሰራልናል? ዋናው ቁም ነገር አሁን ያሉበት ነው፡፡ እንዲያውም ከታሪካዊ አመጣጣቸው ይልቅ አገልግሎታቸው ላይ ማተኮር ይሻላል፡፡ የዋፋይ አገልግሎት በአጭሩ የኢንተርኔት አገልግሎት ማለት ነው፡፡ የኢንተርኔት አገልግሎት ማለት በረጅሙ ዓለምን የመዞር አገልግሎት ማለት ነው፡፡
የምር ግን የስብሰባ ዋና ዓላማ ምንድነው? ይሄ ያን ያህል ውስብስብና ሰፊ ማብራሪያ የሚጠይቅ አይመስለኝም፡፡ የስብሰባ ዋና ዓላማ በአንድ ጉዳይ ላይ በጋራ ለመወያየት የሚደረግ ውይይት ነው፡፡ በዚህ ስበሰባ ውስጥ ደግሞ መደማመጥና ሀሳብ መለዋወጥ የግድ ነው፡፡ ያ ሁሉ ተሰብሳቢ በርካታ ባለጉዳይ የሚያስተናግድበትን ሥራ ዘግቶ ነው የመጣው፡፡ ምክንያቱም በስብሰባው ላይ ተወያይተው ለሆነ ጉዳይ መፍትሔ መምጣት ስላለበት ማለት ነው፡፡
አሁን አሁን ስብሰባዎቻችን ብዙ እያስተዛዘቡን ነው፡፡ በተሰብሳቢዎች ሰዓት ማርፈድ የሚባክነው ጊዜና በገባ ወጣ ትርምስ ሌሎችን መረበሽ የተለመዱ ቋሚ ትዕይንቶች ናቸው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን አንድ የሚገርመኝ ነገር አለ፡፡ በትልልቅ የስብሰባ ቦታዎች ላይ ዋይፋይ ተገጥሟል፡፡ ይሄ ማለት እኮ ‹‹ስብሰባውን ተውትና ፌስቡክ ተተቀሙ›› ከማለት አይተናነስም፡፡ ደግሞ እኮ በጣም የሚገርማችሁ ይሄ የሚሆነው በትልልቅ የስብሰባ ቦታዎች ላይ ነው፤ ዓለም አቀፍ ጉዳይ በሚወራባቸው ስብሰባዎች ላይ ሳይቀር፡፡
ገና ወደ አዳራሹ እንደገባችሁ የቤቱ የዋይፋይ ምስጢር ቁጥር ከፊት ለፊት ይቀመጣል፡፡ ይህኔ እንግዲህ ሌላ ቦታ ኔትዎርክ ሲያስቸግረው የነበረ ሁሉ ጥሙን የሚወጣው እዚያ ነው፡፡ ከኢንተርኔት ማውረድ የሚፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ የሚያወርድ የዚያን ዕለት ነው፡፡ በዚያ ላይ ነፃ ስለሆነ ሳንቲም አለመቁረጡም ሌላው ቀልብ ሳቢ ነገር ነው፡፡ እዚህ ስብሰባ ውስጥ ያለ ሰው ጆሮውን ቢቆርጡት እኮ አይሰማም፡፡
በነገራችን ላይ ስብሰባ ውስጥ ዋይፋይ የሚያስፈልግበት አንድ ሌላ አስገዳች ችግር ደግሞ አለ፡፡ ስብሰባዎች በተባለላቸው ሰዓት ተካሂደው አያውቁም፤ ቀድሞ የደረሰ ሰው የሚደርስበትን መጉላላት አስቡት! ስለዚህ በነፃ ኢንተርኔት መካስ አለበት ይሄ ሰውየ፡፡ እናም ምን ለማለት ፈልጌ መሰላችሁ? ዋይፋይ ስብሰባ ቦታ ውስጥ ሙሉ በሙሉ አያስፈልግም ሳይሆን አጠቃቀሙ ግን አልታወቀበትም፤ ወይም የሆነ ሌላ ዘዴ ሊፈጠርለት ይገባል፡፡ ‹‹አንተ ብትሆን ምን ታደርግ ነበር?›› አትሉኝም!
እንደኔ እንደኔ ልክ ስብሰባው ሲጀመር የዋይፋይ አገልግሎት መቋረጥ አለበት፤ ወይም ሌላ የክልከላ ዘዴ መኖር አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ስብሰባው እየተካሄደ ያለው ለመርሃ ግብር ማሟያና ለሪፖርት ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ መድረክ መሪውም ማንም እንደማይሰማው እያወቀ ከሆነ የሚያወራ እሱም የይውጣልኝ ነው እየሰራ ያለው፡፡ እዚያ ላይ እኮ አገራዊ ጉዳይ ነው እየተወራ ያለው፡፡ መድረክ ላይ ምን እንደቀረበ ያልሰማ ተሳታፊ ምን ብሎ አስታየት ሊሰጥ ይችላል?
ያለመደማመጥ ነገር ቀላል ችግር እንዳይመ ስላችሁ፡፡ አለመደማመጥን ካነሳነው አይቀር ሌላም እንጥቀስ፡፡ ስብሰባዎች ላይ ሰዓት የሚባክነው ባለመደማመጥ ነው፡፡ በተለይም ትልቅ አዳራሽና ብዙ ተሰብሳቢ ባለበት ይሄ ችግር ይከፋል፡፡ አንድ ተናጋሪ ሲናገር ተሳታፊው ማዳመጥ አለበት፡፡ ምን እንደተባለ ካልሰማ ‹‹እከሌ እንዳለው›› እንኳን ሳይል የመጀሪያው ተናጋሪ የተናገረውን ይደግማል ማለት ነው፡፡
በእርግጥ ሰምተውም የሚደግሙ አሉ፡፡ ለምሳሌ ‹‹እኔ እንኳን አቶ እገሌ በተናገረው ላይ ለመጨመር ያህል ነው›› ብሎ ይጀምርና ምንም ሳይጨምር የአቶ እገሌን ንግግር ይደግመዋል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ‹‹እኔ አቶ እገሌ በተናገረው እስማማለሁ›› ብሎ ሀሳቡን ይጨርሳል፡፡ ሀሳቡን አቶ እገሌ ከተናገረለት ለምን ጊዜ ያባክናል? አድናቆቱን ሲወጡ ይግለጽለት፡፡
ከዚህ ሁሉ በላይ ግን አስቸጋሪው ሳይሰሙ የሚናገሩት ናቸው፡፡ መድረክ መሪው ‹‹እባካችሁ የተነሳ ሀሳብ አትድገሙ›› እያለ ደጋግሞ ይናገራል፤ እሱን ራሱ ማን ሰምቶት፡፡ መድረክ መሪው ባስ ሲልበት ተናጋሪውን በማቋረጥ ‹‹እሱ ሀሳብ ተነስቷል›› ሲለው ካፈርኩ አይመልሰኝ በሚል ‹‹ቆይ ልጨርስ›› እያለ የተነገረውን ሁሉ ደግሞ ይናገራል፡፡ እንግዲህ አስቡት በጥሞና ያላዳመጠ ሁሉ ሲናገር ሀሳቦች እጥፍ እጥፍ ሊደገሙ ነው ማለት ነው፡፡ ሌሎች ሲያጨበጭቡም አብሮ ያጨበጭባል፡፡ እየሰማ ነው እንዲባል፡፡
ወደ ዋይፋይ እንመለስ፡፡ በአንድ ትልቅ አዳራሽ ውስጥ የታዘብኩትን ነው የምነግራችሁ፡፡ ስብሰባው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ነው፡፡ በየጠረጴዛው ላይ ላፕቶፕ ተቀምጧል፡፡ መጀመሪያ ሳየው ለስብሰባው የግድ አስፈላጊ የሆነ ነገር ነበር የመሰለኝ፡፡ በኋላ ውይይቱ ሲጀመር ግን የሚጠቀሙት ነገር ከስብሰባው ጋር ምንም የሚገናኝ አይደለም፡፡ አንዳንዱ ፌስቡክ ይጠቀማል፤ አንዳንዱ ቪዲዮ ያየል፣ አንዳንዱ ሌላ ጽሑፍ ያነባል፤ መድረክ ላይ የሚባለውን ነገር የሚሰማው ከፊቱ ላፕቶፕ የሌለ ሰው ብቻ ነበር፡፡ ላፕቶፕ ከሌላቸው ሰዎች ውስጥም በራሱ ስልክ የሚጠቀመው ቀላል አይምሰላችሁ፡፡
ሌላው የዋይፋይ ትዝብቴ ደግሞ በጋዜጠኞች ላይ የማየው ነው፡፡ አንድ ጋዜጠኛ ሊዘግብ የሄደበትን ጉዳይ በጥሞና ነው መከታተል ያለበት፡፡ ምናልባት እሱ የፈለገው የራሱ ‹‹አንግል›› ይኖረው ይሆናል፡፡ ምንም ይሁን ምን ግን ስብሰባው ላይ የተባለውን ነገር ሳይሰማ የራሱን ጥያቄ እንኳን መጠየቅ አይችልም፡፡ ያ የሚያናግረው ሰው እንኳን ‹‹ውይይቱ ላይ እንደሰማኸው…›› እያለ ነው የሚያወራ፡፡ ይህኔ ጋዜጠኛው የተባለውን አልሰማም፡፡ ለዚህ እኮ ነው ጋዜጠኞች ጥያቄ ሲጠይቁ ‹‹የዛሬው ስብሰባ ስለምንድን ነበር?›› ብለው የሚጀምሩት፡፡
የምር የዋይፋይ ነገር ቦታ ሊመረጥለት ይገባል፡፡ አንድ ስብሰባ የጋራ መደማመጥ ከሌለበት ለምንድነው ጊዜ የሚባክነው? ምን ጊዜ ብቻ ያ ሰብሰባ እኮ ብዙ ብር ወጪ የተደረገበት ነው፡፡ ስለዚህ ለውይይት የሚጠራው ሰው የማይከታተለው ከሆነ ብክነት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡
አሁን እንግዲህ አከራካሪው ነገር ‹‹እንዴት ትላልቅ የስብሰባ ቦታ ላይ ዋይፋይ ይጥፋ? ይባላል›› የሚለው ነው፡፡ እርግጥ ነው ዋይፋይ በራሱ እኮ ችግር የለበትም፡፡ እሱ የተሰራበትን አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ እኛ ግን አጠቃቀሙን ካልቻልንበት ያለው አማራጭ አለመኖሩ ሊሆን ነው፡፡ አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ያገልግል እንጂ ለመረባበሻማ መሆን የለበትም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ያስቁኛል፡፡ ሆነ የድምጽ ብልጫ የሚያስፈልገው ነገር ካለ እጅ እንዲያወጡ ይቀሰቀሳሉ፡፡
የምርጫ ሀሳቡ ሲሰጥ ለየትኛው ሀሳብ ያውጡ? ከመራጩና ከደጋፊው ይልቅ ድምፀ ተዓቅቦ የሚባለው ይበልጣል ማለት ነው፡፡ ይሄ የሆነው እንግዲህ ምን እንደሆነ ስላልገባው ነው፡፡ በዘፈቀደ ካወጣም የሚፈጠረውን መጭበርበር አስቡት፡፡ እናም ወይ አጠቃቀማችን ይስተካከል ካልሆነም በስብሰባ ቦታ ውስጥ ዋይፋይ ይዘጋ!!!

ዋለልኝ አየለ

Published in መዝናኛ

ወጣት ብርሃኑ ጌታቸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኬሚካል ኢንጂነሪንግ ተመርቋል፡፡ በተመሳሳይ የትምህርት ዘርፍ አብረውት ከተማሩና ከሌላ ዩኒቨርሲቲ ከተመረቁ አምስት ጓደኞቹ ጋር በጋራ ለመስራት ይደራጃሉ፡፡ በተመረቁበት የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ዘርፍ እውቀትን በመጠቀም ችግር ፈቺ እንደሆነ ያመኑበትን ማጣበቂያ(ማስቲሽ) ለማምረት እቅድ አውጥተው በአካባቢያቸው ወዳለው የስራ ዕድል ፈጠራ ቢሮ ያቀናሉ፡፡
ላቀዱት አዲስ የስራ ሀሳብ የሚሆን ግብዓት በአገር ውስጥ እንደሚያገኙና በቂ የገበያ ፍላጎት መኖሩን አረጋገጡ፡፡ ይህን በማድረግም ለቢሮው ቢያቀርቡም የሚረዳቸው አላገኙም፡፡ የመስሪያ ቦታና ብድር ለማግኘት የስራ ዕድል ፈጠራ ቢሮው በመመላለስ ብቻ ሶስት ዓመት እንዳለፋቸው ወጣት ብርሃኑ ይናገራል፡፡ ‹‹ አዋጭ የሆነ አዲስ የስራ ሀሳብ ይዘን ለቢሮው ሃላፊዎች በተለያየ መንገድ ለማስረዳት ብንሞክርም እድል የሚሰጠን አጥተናል›› ይላል፡፡
‹‹እኛን መደገፉ ቀርቶ ያመጣነውን ሀሳብ እንኳን ለመረዳት የሚፈልግ ኃላፊ ባገኘን›› የሚለው ወጣቱ፤ ወጣቶች ለሚያመጡት አዲስ የስራ ፈጠራ ሀሳብ ትኩረት ሰጥቶ ለማገዝ የሚሰራ እንደሌለ ይናገራል፡፡ የስራ እድል ፈጠራ ቢሮዎች አሰራር ወጣቶችን ለስራ የማያነሳሳ፣ ግልጽና አበረታች ያልሆነ፣ የስራ ሀሳቡም ውጤታማ እንዲሆን የማያግዝ መሆኑን ወጣት ብርሃኑ ያስረዳል፡፡ በስራ ዕድል ፈጠራ ቢሮዎች ያሉ ባለሙያዎችም ወጣቶች ለመደራጀት፣ ብድርና የመስሪያ ቦታ ለማግኘት ማሟላት ያለባቸውን መስፈርቶች በአግባቡ የማያስረዱ መሆናቸውን ይገልፃል፡፡ በዚህም የተነሳ ያለ መፍትሄ ከማመላለሳቸውም በላይ አዲስ የስራ ፈጠራ ሀሳብን በትክክል ሳይረዱ አዋጭ አይደለም የሚል ምላሽ እንደሚሰጡ ጠቁሟል፡፡ ይህም ወጣቶችን ተስፋ እያስቆረጠ ነው፡፡
በወጣቶች የስራ ፈጠራ ቢሮዎች ከገጠማት በመነሳት ‹‹ወጣቶች አዳዲስ የስራ ፈጠራ ሀሳብ ሲያመጡ እንደሚበረታቱ የሚነገረው ከቃል ያልዘለለ ነው›› የምትለው ደግሞ ወጣት ትዝታ ተረፈ ነች፡፡ ወጣት ትዝታ ከንፋስ ስልክ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋም በኦንሳይት ቢዩልዲንግ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ተመርቃለች፡፡ ትዝታና ጓደኞቿ የድንጋይ ቅርጻ ቅርጽ ስራ ለመስራት ተደራጅተዋል፡፡
ወጣት ትዝታ እንደምትናገረው የስራ ፈጠራ ሀሳባቸው ለጥቃቅንና አነስተኛ አዲስ በመሆኑ ስልጠናም ምዘናም የለውም፡፡ የስራ ሃሳባቸውን ለስራ ፈጠራ ቢሮ ለማስረዳት ብቻ ብዙ ጊዜ ከመፍጀቱም በላይ አብዛኛው የቢሮ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የስራ ሃሳባቸውን ለመረዳት ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ኃላፊዎች ሀሳባቸውን ለመስማት እና ለማነጋገር ፈቃደኛ የሚሆኑት በንዴትና በኃይለ ቃል ሲናገሩና በተደጋጋሚ ቢሮ በመሄድ ተስፋ እንደማይቆርጡ ሲያዩ ብቻ ነው፡፡ ወጣቶች የሚያመጡት ሀሳብ ምን ያህል የስራ ዕድል እንደሚፈጥር፣ ምን ያህል የህብረተሰቡን ችግር እንደሚቀርፍና ምን ያህል ውጤታማ እንደሚሆን ተረድቶ ለማገልገል የሚሰራ የለም፡፡
‹‹በተቀመጠው አሰራር መሰረት ሊያገለግሉን የሚሞክሩ ባለሙያዎች ቢኖሩ እንኳን ሊረዱን የሞከሩበት መንገድ ወደ ፖለቲካ እሳቤ ይቀየራል፡፡ የቢሮው ኃላፊዎች የሙያ ብቃት ኖሯቸው ሳይሆን ከፖለቲካ ተሳትፏቸው አንጻር የተመደቡ ናቸው፡፡ የቢሮው ባለሙያዎቹም ለስራ ፈጠራ ስራው ድጋፍ ከመስጠት አንጻር ሳይሆን ከፖለቲካ አንጻር ስለሚገመገሙ ለወጣቶች አዲስ የስራ ሃሳብ ኃላፊነትን መውሰድ አይፈልጉም›› በማለት የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ቢሮው የስራ ዕድል ፈጠራን ለማስፋፋት እስከማይመስል ድረስ በማያሰሩ መመሪያዎች የታጠረ መሆኑን ትዝታ ትናገራለች፡፡
ከአንድ ዓመት የቢሮ ምልልስ በኋላ የመስሪያ ቦታ እንደተሰጣቸውና ስራ ሳይጀምሩም ሁለት አመት እንደሞላቸው ወጣት ትዝታ በቁጭት ትገልፃለች፡፡ ያለው አሰራር ግልጽነት የጎደለውና ከአሰራር ውጪ በኃላፊዎች ፈቃድ ላይ የተመሰረተ፣ አዳዲስ የስራ ሃሳቦች እንዲመጡና ውጤታማ እንዲሆን የማያግዝ፣ ተስፋ አስቆራጭ እና የቢሮው ባለሙያዎች ተነሳሽነት የጎደላቸውና ስልቹ መሆናቸውን ትጠቁማለች፡፡
‹‹ተገቢ ባልሆነ መንገድ እየተስተናገድን ያለነው ወጣቶችን የሚያንገላታውን አሰራር ለማስተካከል ከባድ ሆኖ አይደለም›› በማለት ለቦታው የሚመጥኑ እውቀትና ቅንነት ያላቸው፣ ከፖለቲካ አመለካከት ነጻ ለሆኑ ሰዎች ኃላፊነት በመስጠት ችግሩን መቅረፍ እንደሚቻልም ነው ወጣት ትዝታ የገለፀችው፡፡
የፌዴራል የከተሞች ስራ እድል ፈጠራ እና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የኢንተርፕራይዞች ልማት ዳይሬክተር አቶ በለጠ ባላ ተቋሙ በስራ እድል ፈጠራ ላይ መንግስታዊ ድጋፎችን የመስጠት፣ የአሰራር ስርዓት የማዘጋጀት፣ የማሻሻል፣ የመምራት የመደገፍና የመከታተል ኃላፊነት እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ የስራ እድል ፈጠራ ማነቆዎችን የሚፈታ እና ወጣቶች የሚያመጡት አዲስ የስራ ሃሳብ የሚስተናገድበት አሰራር መኖሩን ያስረዳሉ፡፡ ይህም ሆኖ በወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ጉድለቶች መኖራቸውን አልሸሸጉም፡፡
በክፍለ ከተሞችና በወረዳ የስራ እድል ፈጠራ ቢሮዎች አሰራር ሲፈተሸ ወጣቶች በአግባቡ የስራ ዕድል ፈጠራ ድጋፍ እያገኙ አለመሆኑ መረጋገጡን አቶ በለጠ ያመለክታሉ፡፡ የስራ ዕድል ፈጠራ አሰራር ወጥ አለመሆኑ፣ የስራ ፈጠራ ሀሳብ አረዳድ አለመኖር፣ ያለመናበብ፣ የተሟላ ግንዛቤ አለመኖር ሥራው በአግባቡ እንዳይሰራ አድርጓል ብለዋል፡፡
አቶ በለጠ እንደሚናገሩት፤ በስራ እድል ፈጠራ ቢሮዎች የሚገኙ ኃላፊዎችም የስራ እድል ፈጠራ ምንነትን ተረድተው በአግባቡ የመምራት ግዴታቸውን እየተወጡ አይደለም፡፡ አዲስ ሀሳብ ይዘው የሚመጡ ወጣቶችን ማመላለስ፣ አዳዲስ የስራ ፈጠራ ሀሳቦቹን በአግባቡ ያለመረዳት፣ በስራ እድል ፈጠራ ቢሮ ኃላፊዎችና የቢሮው ባለሙያዎች በትክክል ከስራ ፈጠራ ጋር የተያያዘ ዕውቀት ያለመኖር፣ ስራውን በቅልጥፍና አለመምራትና በቂ ድጋፍ አለማድረግን የመሳሰሉ ችግሮች ተበራክተዋል፡፡
‹‹የንግድ ሀሳብ ላይ የድጋፍና ክትትል ስራ መስራት ያለበት ከንግድ ጋር የተያያዘ እውቀት ያለው ባለሙያ ነው፡፡ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ደግሞ ተያያዥ እውቀት ያለው ባለሙያ መሆን ነበረበት›› በማለት በስራ እድል ፈጠራ አሰራር መዋቅር ውስጥ ስራውን ለማስተባበር በሚል የተመደቡ ባለሙያዎች እንጂ ቦታው ለሚያስፈልገው ለስራ እድልና የንግድ ስራ ጋር እውቀት ያላቸው አለመሆናቸውንም አቶ በለጠ ይገልጻሉ፡፡ ለዚህም ‹‹በስራ ዕድል ፈጠራ ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉ ለተመደቡት ባለሙያዎች እኛ ድጋፍ እያደረግን ነው›› የሚሉ ኢንተርፕራይዞች መኖራቸውን በመጠቆም ክፍተቱን ያስረዳሉ፡፡
አቶ በለጠ እንደሚናገሩት አብዛኛው የስራ እድል ፈጠራ ኃላፊና ባለሙያ የስራ መመሪያውን አያነቡም፡፡ ኃላፊዎቹ መመሪያው ምን እንደሆነ በትክክል ሳያውቁ ውሳኔ ይሰጣሉ፡፡ መመሪያውን ለማወቅም ጥረት አያደርጉም፡፡ ወጣቶችን የሚያንገላቱና በአግባቡ ምላሽ መስጠት ባለመቻላቸው ምክንያት በፖለቲካ ሰበብ አደባብሰው ለማለፍ የሚሞክሩም አሉ፡፡
በቀጣይ የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራን ከእንግልት ለመገላገል ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት እቅድ መኖሩን አቶ በለጠ ጠቁመዋል፡፡ ወጣቶች በትምህርት ተቋማት ውስጥ እንዳሉ የሚያመጡትን የስራ ሃሳብ ሳይንገላቱ አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያገኙበት አሰራር ከትምህርት ተቋሞቹ ጋር በጋራ ለመፍጠር በእቅድ መያዙን አመልክተዋል፡፡
በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የወጣቶች ጉዳይ ማካተት እና የስራ እድል ፈጠራ ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ብዛ የወጣቶች ጉዳይ በሁሉም ሴክተር ተቋማት እንዲካተት የማድረግ ስራ እንደሚሰራ ይናገራሉ፡፡ የተቋማት እንቅስቃሴ በእያንዳንዱ እቅድ፣ ፕሮጀክት፣ ፕሮግራምና ፖሊሲያቸው ውስጥ ወጣቶችን ያካተተ እንዲሆን የመከታተልና የመደገፍ ሥራ እንደሚያደርግ ይናገራሉ፡፡ ወጣቶች በስራ እድል ፈጠራ ተጠቃሚነት ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ሀሳብ እንደሚያቀርቡም ያስረዳሉ፡፡
አቶ መንግስቱ ወጣቶች የስራ ሃሳብ ሲያመጡ እንዴት እንደሚደራጁ፣ እቅድ እንደሚያወጡና የስራ ፈጠራ ሀሳባቸው ውጤታማ እንዲሆን ድጋፍ የሚያደርግላቸው አካል እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡ ወጣቶች አዳዲስ የስራ ሃሳቦችን ሲያመጡ ሃሳባቸው ወደ ስራ እንዲቀየር ድጋፍ የሚያደርግ አካል ስለማያገኙ እንደሚቸገሩና ወጣቶችን የመደገፍ ስራው ተሰርቷል ብለው እንደማያምኑም ይገልጻሉ፡፡ የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ሙሉ ለሙሉ ከፖለቲካ ነጻ መሆን እንዳለበት ጠቁመው፤ ገና ወደ ስራ የሚገቡ ወጣቶችን ከጅምሩ በፖለቲካዊ እሳቤ ማደናቀፍ እንደማይገባ ያስገነዝባሉ፡፡
የወጣቶችን የስራ እድል ፈጠራ ድጋፍ፣ የብድርና የመስሪያ ቦታ የማግኘት መብታቸውን የሚነፍጉ፣ ወጣቶችን በማማረር ተስፋ እንዲቆርጡ የሚያደርጉ ባለሙያዎች እንዳሉ እየታወቀ ችግሩን በአፋጣኝ ያለመቅረፍ ድክመት እንዳለ ማስተዋላቸውን አቶ መንግስቱ ይናገራሉ፡፡ ‹‹በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ቴክኒክና ሙያ ስልጠናዎች የሚሰጡ ትምህርቶች በአብዛኛው በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ ነው፡፡ በስራ እድል ፈጠራ ቢሮዎች ግን የተፈጥሮ ሳይንስ እውቀት ያለው ባለሙያ ማግኘት ይከብዳል›› በማለት አሰራሩ ወጥና አበረታች መሆን እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡
አቶ መንግስቱ ለችግሩ መፍትሄ ነው የሚሉትን ጠቁመዋል፡፡ የወጣቶችን አዳዲስ የስራ ፈጠራ ሀሳብ የሚቀበልና ሀሳባቸውን አበልጽጎ ውጤታማ የሚያደርግ አሰራር መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ከፌዴራል አንስቶ እስከ ወረዳ በሚገኙ የስራ እድል ፈጠራ ቢሮዎች አሰራሩ በእውቀት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት፡፡ ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉ የሚመደቡ ባለሙያዎች የስራ ፈጠራ ሃሳቦችን የሚረዱ፣ ለወጣቶች የስራ እድል እንዲፈጠር በቅንነት ተግተው የሚሰሩና በትክክል ድጋፍ መስጠት የሚችሉ ሊሆኑ ይገባል፡፡ በሁሉም የሙያ ዘርፍ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል እውቀት ያላቸው ባለሙያዎችን መመደብ አስቸጋሪ ቢሆን እንኳን ቢያንስ ስለ ስራ ፈጠራና ሃሳብን ተረድቶ የማበልጸግ እውቀትና አቅም ያላቸው ባለሙያዎች ሊሆኑ ግድ ይላል፡፡

ሰላማዊት ንጉሴ

Published in ማህበራዊ
Thursday, 10 May 2018 19:36

የስደት ሌላኛው መዘዝ

በህገ ወጥ ስደት ምክንያት በርካታ ኢትዮጵያዊያን በየባህሩና በየበረሃው የአውሬ ራት ሆነው ቀርተዋል፡፡ ወላጆቻቸው ኑሮን ለማሸነፍ ብለው ከሀገር የተሰደዱባቸው በርካታ ህጻናትም ያለ አባትና እናት ለማደግ ተገደዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉ ወላጆችም ልጆቻቸውን ለአስከፊው ስደት ገብረው ጧሪ ቀባሪ አጥተዋል፡፡ጥቂት የማይባሉ ግለሰቦች ደግሞ ልጆቻቸውን ወደ ተለያዩ ሀገራት እንወስዳለን ለሚሉ ህገ ወጥ ደላሎች ያላቸውን መሬትና ቤት ሸጠው ገንዘብ አስረክበው ችግር ውስጥ ወድቀዋል፡፡ 

የተለያዩ እርምጃዎች እየተወዱበትና ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገም ቢሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እያደገ የመጣው ይኸው ህገወጥ ስደት ታዲያ ዛሬ ዛሬ ደግሞ ከማህበራዊ ቀውሱ ባሻገር ሌላም መዘዝ ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ ይኸውም በተለይ በርካታ ወጣቶቿን ወደ ደቡብ አፍሪካ እያጎረፈች ባለችው በደቡብ ክልሏ ሃድያ ዞን የተከሰተ ጉዳይ ነው፡፡ በዞኑ ምንአልባትም በየአንዳንዱ ቤተሰብ ቢያንስ አንድ ወጣት የህገወጥ ስደቱ ሰለባ ነው፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ አሁን ደግሞ ጉዳዩ ለጎሳ ግጭትም ሰበብ ሆኗል፡፡ የአካባቢው ሽማግሌዎች በህገወጥ ስደቱ ምክንያት እየተፈጠረ ያለው የጎሳ ግጭት ችላ ከተባለና በዚህ ከቀጠለ ከፍተኛ ቀውስ ያስከትላል የሚል ስጋት አላቸው፡፡
በዚሁ ዞን በሌሞ ወረዳ የሹርሞ ዳጮ ቀበሌ ነዋሪ ገራድ መንገሻ ህቤቦ እንደሚናገሩት፤ የግጭቱ መነሻ ደቡብ አፍሪካ ባሉ የአካባቢው ተወላጆች መካከል የሚከሰት ሲሆን በዋናነት በስራቸው ያልተሳካላቸውና ሃብት ማፍራት ያልቻሉት ስደተኞች ከቤተሰብ የሚደርስባቸውን ጫና በመስጋት የተሳካላቸውን ወገኖቻቸውን ሃብት በመዝረፍና በመደብደብ እያስከተሉት ያሉት ጠባሳ ከተሰደዱባት አገር ባሻገር በአገር ባሉ ወላጆችና ጎሳዎች መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡
በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ በአካባቢው ተወላጆች መካከል በሚፈጠር አለመግባባት፣ ግጭትና ሞት ምክንያት በአካባቢው የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት በወር ሁለት ወይም ሶስት ጊዜ ስብሰባ እንደሚቀመጡ ይናገራሉ፡፡«በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ለቤተሰቦቻቸውና ለጎሳቸው አባላት በስልክ ደውለው የእከሌ ጎሳ አባል የሆነው ግለሰብ ጉዳት አድርሶብኛል ወይም አደርስብሃለሁ ብሎ ዝቷል ብለው ማሳወቃቸውን ተከትሎ ወላጆቻቸው እዚህ ባለ የሌላኛው ስደተኛ ወገን ላይ በቂም በቀል ይዘምታል» ይላሉ፡፡ ይህም በአካባቢው ሁከት አለመረጋጋት እንዲነግስ ምክንያት ሆኗል ባይ ናቸው፡፡
በደቡብ አፍሪካ ምን እንደተፈጠረ የማያውቁ ‹‹የዘራፊ ወይም የገዳይ›› ቤተሰብ ወይም ዘመድ ናቸው በሚባሉ ግለሰቦች ላይ የዝርፊያ፣ ቤት የማቃጠልና ግድያ የመፈጸም ሙከራዎች እንደሚደረግ ይጠቅሳሉ፡፡ ይህም አብዛኛውን ጊዜ ባልተረጋገጠ ወሬ ‹‹ወንድምህ ወንድሜን፣ ልጅህ ልጄን ወይም የጎሳህ አባል የጎሳዬን አባል ዘርፎ፣ ደብድቦ ወይም ገድሎ አንተ በሰላም አትኖርም›› በሚል እንደሚነሳ ያመለክታሉ፡፡
ገራድ መንገሻ እንደሚሉት፤ በአሁኑ ወቅት የበዳይን ቤተሰብ ወይም ጎሳ እንገድላለን፣ ንብረት እንዘርፋለን፣ ቤትም እናቃጥላለን ብለው የሚነሱትን አደብ በማስያዝ፣ የሽማግሌዎችን ትዕዛዝ የማይቀበሉትን በመገሰፅና በማውገዝ ችግሩን ለማብረድ ሽማግሌዎች ጥረት እያደረጉ ናቸው፡፡ በተቻለ አቅምም ንብረት እንዳይወድም፣ ቤት እንዳይቃጠልና ግድያ እንዳይፈጸም ሽማግሌዎቹ ተመሳሳይ አቋም ይዘው ችግሩን ለመቆጣጠር እየሰሩ ነው፡፡ ከሽማግሌዎች አቅም በላይ የሚሆኑትን ለአካባቢው ጸጥታ በማሳወቅ ችግሩ እልባት እንዲያገኝ ጥረት እያደረጉም ይገኛሉ፡፡
ችግሩ በሌሞ ወረዳ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የዞኑ ወረዳዎች ላይ መከሰቱን የሚጠቅሱት የአገር ሽማግሌው ከሚኖሩባት ቀዬ ባሻገር በሌሎችም አካባቢዎች ከሚኖሩ ሽማግሌዎች ጋር በመተባበር አስቀድሞ የመከላከልና የተከሰተውንም ግጭት የማብረድና ስራ እየሰሩ መሆናቸውን ነው ያመለከቱት፡፡ ሽማግሌዎች የችግሩ ዋነኛ ምንጭ የሆነውን ህገ ወጥ ስደት ለመከላከል በየስብሰባው አጀንዳ አድርገው ይወያዩበታል፤ የህብረተሰቡን አስተሳሰብ ለመቀየር ጥረት ከማድረግ ባሻገር ህገ ወጥ ደላሎችን ያወግዛሉ፡፡ ያላቸውን አንጡራ ሀብት ሸጠው ለህገ ወጥ ስደት ልጆቻቸውን የሚያዘጋጁ አባቶችንም በመምከር ልጆቻቸው እዚሁ ሰርተው እንዲለወጡ ምክራቸውን እንደሚለግሷቸው ነው ያስረዱት፡፡ በዚህም ከዚህ ቀደም በአካባቢው ወጣቶችን በህገወጥ መረባቸው ያጠምዱ የነበሩ ህገወጥ ደላሎችም ቁጥራቸው እየተመናመነ መምጣቱን ያመለክታሉ፡፡ ይሁንና መቀመጫቸውን በውጭ ሀገራት አድርገው አጥፊ ሚናቸውን መቀጠላቸው ይናገራሉ፡፡ ይህም ህገወጥ ስደትን ለመከላከል የተደረገውን ጥረት ያክል ውጤት ማስመዝገብ እንዳልተቻለ ይገልፃሉ፡፡
«አብዛኛውን ጊዜ ለግጭቱ መንስኤ የሚሆነው በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ከሀገር ቤት ወደዚያ መሄድ የሚፈልግ ተጓዥ ወይም የተጓዡ ቤተሰብ መሬት እንዲሰጠውና እሱ ደግሞ ተጓዡን ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚያስገባ ገንዘብ ለደላላ ለመስጠትና በደቡብ አፍሪካ ተቀብሎ ስራ ለማስጀመር ይዋዋላሉ» የሚሉት ደግሞ የወረዳው የጸጥታና አስተዳደር ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ተሻለ የሱፍ ናቸው፡፡ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩት ይህን የሚያደርጉትም የመሬት ዋጋ ከዕለት ወደ ዕለት እንደሚጨምር ስለተረዱት መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ይህም ደግሞ በአካባቢው ህገ ወጥ የመሬት ወረራ ምክንያት እየሆነ መምጣቱንም ያስረዳሉ፡፡
በአጋጣሚ ወደ ደቡብ አፍሪካ የተጓዘው ግለሰብ ከመንገድ የመመለስ፣ ከመታሰር ወይም የመሞት እድል ካጋጠመው ተጓዡ ወይም የተጓዡ ቤተሰብ እቅዱ ስላልተሳካ መሬቱን አንሰጥም የሚሉበት ሁኔታ እንዳለም ያመለክታሉ፡፡ «በደቡብ አፍሪካ ያለው ግለሰብ ደግሞ ገንዘብ ለደላላ ስለሰጠሁ እኔ ገንዘብ አውጥቼ እንዴት መሬቴን አላገኝም በሚል እዚህ ያለው ቤተሰብ ወይም ከከልካዮቹ ጋር ወደ ግጭት እንዲገቡ ያደርጋሉ» ይላሉ፡፡ በተለይም አለመግባባት የተፈጠረው በሁለት ጎሳዎች ተወላጆች መካከል ከሆነ አለመግባባቱን የጎሳ ለማድረግ የሚጥሩ አካላት አሉ፡፡ እንደዚህ አይነት ችግር በወረዳው በተደጋጋሚ እንደሚከሰት ነው አቶ ተሻለ ያብራሩት፡፡
በአሁኑ ወቅት ህገ ወጥ ስደት በአካባቢው ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ቀውስ እያስከተለ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ተሻለ፤ ችግሩን ለመፍታት እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ «በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች መካከል ግጭቶች ሲከሰቱ ወይም የሞት አደጋ ሲያጋጥማቸው የሟቾች ቤተሰብ በጉዳዩ ዙሪያ መረጃ እንዲኖራቸው እየተደረገ ነው» ይላሉ፡፡ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ጉዳት አድርሷል ወይም ገድሏል ተብሎ ወደ ሚጠረጠር ቤተሰብና ጎሳ ሄዶ ግጭት መፍጠር ከተጠያቂነት የማያድን መሆኑን ጠቅሰው፤ ለሚደርሰው ውድመት እያንዳንዱ ተሳታፊ ተጠያቂ መሆኑን አስቀድሞ ህብረተሰቡ እንዲያውቀው መረጃ የማድረስ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡
እንደ አቶ ተሻለ ማብራሪያ፤ የጎሳ ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና የዕድር መሪዎች በየጎሳቸው፣ በየቤተዕምነቱ እና በየዕድሩ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እያስከተለ ያለው ጉዳት ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እንዲሰሩ እየተደረገ ነው፤ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በረጅም ጊዜም በህብረተሰቡ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ወሳኝ በመሆኑ ይህን ለውጥ ለማምጣት የወረዳው ሰራተኛና ማህበራዊ ፅህፈት ቤት፣ ፖሊስና ጸጥታ በጋራ በየአስራ አምስት ቀን ይወያያሉ፡፡ የግንዛቤ ችግር ባለባቸው አካባቢዎችም ጉዳዩን በጋራ በመወያየት እንዲጠራ መግባባት ላይ ለመድርስ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም በደቡብ አፍሪካ የሚፈጠሩ ግጭቶች በሀገር ቤት ጎሳዊ መልክ እንዲላበሱ በሚያደርጉ ግለሰቦች ህጋዊ እርምጃ አለመወሰዱን አቶ ተሻለ ይገልፃሉ፡፡ በግለሰቦች ላይ ለምን ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እንዳልተቻለ ሲጠቅሱም «ከዚህ ቀደም ጉዳዩ በሽምግልና በመያዙና ሞትን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ በአካባቢው በአብዛኛው በሽምግልና የመጨረስ ልምድ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው በመሆኑ እልባት ሳያገኝም ወደ ክስ መሄዱ ተገቢ ባለመሆኑ እርምጃው እንዲዘገይ ተደርጓል» ይላሉ፡፡ የአካበቢው ሽማግሌዎች ጥሩ የሚባል ስራ እየሰሩ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን ግንዛቤ የማስጨበጡ ስራ በአግባቡ በሚፈለገው ልክ በመሰራቱ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እንደሚጀመር ነው ያመለከቱት፡፡
የሀድያ ዞን ጸጥታ መምሪያ ሀላፊ አቶ ጸጋዬ ኤርቲሮ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ዜጎች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በአገር ውስጥ ለጎሳዎች ግጭት የመሆን መጠኑ በአሁኑ ወቅት እያሻቀበ ይገኛል፡፡ በተለይም ከሶስት አመት ወዲህ ችግሩ እየተባባሰ በመምጣቱ ለአገርም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
«የዞኑ የጸጥታ መዋቅር ከደቡብ አፍሪካ በሚናፈሱ አሉባልታዎች ምክንያት ግጭቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ ተብለው ስለሚጠረጠሩ አከባቢዎች አስቀድሞ መረጃ ለማግኘት በንቃት እየተንቀሳቀሰ ነው» የሚሉት የመምሪያ ሃላፊው፤ መረጃውን በቅድሚያ በማግኘት ግጭት እንዳይከሰት የመከላከል ስራ በስፋት እየተሰራ መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡ በቀጣይ ግጭቶችን የጎሳ መልክ ለማስያዝ ጥረት በሚያደርጉት ላይ ህጋዊ እርምጃዎች እንደሚወሰድም ነው ያመለከቱት፡፡
አቶ ጸጋዬ እንዳብራሩት፤ የዞኑ ጸጥታ መዋቅር ከህብረተሰቡ፣ ከሽማግሌዎች፣ ከጎሳ መሪዎች፣ ከሀይማኖት አባቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ጋር በመሆን ችግሩ ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይደርስ እየሰራ ነው፡፡ በተለይም በአሉባልታ ወሬ ህዝቡ ወደ ግጭት እንዳይገባ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች ላይ በስፋት እየተከናወነ ነው የሚገኘው፡፡

መላኩ ኤሮሴ

 

 የሠላም ዲፕሎማሲ

 

ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ፋና ወጊ አገር ናት። በዚህ ረገድ ያላትን መልካም ተሞክሮ ማካፈል የሚያስችልም አቅም ገንብታለች። አገሪቱ የምትከተለው ፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀር ሥርዓት ሠላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን ከማረጋገጥ አኳያ የቱን ያህል ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ብሎም ለቀጣናው እንደጠቀመ መረዳት ቀላል ነው። ይህም የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ከፍታ ምክንያት መሆኑን መረዳት ይቻላል።

ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ በውስጧ ሠላም የፈጠረች አገር ናት። ጎረቤቶቿም ቢሆኑ ሠላማቸው እንዳይናጋ ከመጠበቅ አንፃር በብርቱ ጥራለች። እየከወነቻቸው ያሉ በርካታ ውጤታማ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች ለውጤታማነቷ ሌላው ምስክሮች ናቸው። ኢትዮጵያ ከ27 ዓመታት በላይ የራሷን ሠላም በፅኑ መሠረት ላይ ማቆም የሚያስችል ቁመና ፈጥራለች። በዚህም ከራሷ አልፎ የአጎራባቾቿን ሠላም መጠበቅ እንደምትችል በይፋ አሳይታለች። ይህ ሁኔታ የኢትዮጵያ የሠላም ዲፕሎማሲ ከፍታን አመላካች መሆኑ ግልፅ ነው።


በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የአደራዳሪነት ሚና እየጨመረ ሄዷል። የዲፕሎማሲ ድሉ በንጉሱ ዘመነ መንግሥት ወቅትም የነበረ ነው፤ ተቋማዊና በሰለጠነ መንገድ እየተመራ ይበልጥ ተቀባይነቱም እየጎላና እየደመቀ የመጣው ግን በኢፌዴሪ መንግሥት መሆኑ እውነት ነው። ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ድምፅ እስከመሆን የበቃችው በኢፌዴሪ መንግሥት ነው።
ኢትዮጵያ አፍሪካን ብሎም ዓለምን እያስጨነቀ በመጣው የአየር ንብረት ለውጥ የሙቀት መጠን መጨመር ጉዳይ ላይ የአፍሪካዊያን ልሣን ሆና ብቅ ያለችውም በዚሁ መንግሥት ነው። የመፍትሄው አካል ሆናም በቅድሚያ በራሷ የአረንጓዴ ልማት አቅጣጫን በአርአያነት ያሳየችውም በኢፌዴሪ መንግሥት ነው። ይህ ሁሉ ተግባሯም በሌሎች ዘንድ ያላት ተቀባይነት ከፍ እንዲል ረድቷታል። ተቀባይነቷም እንዲጎለብት አግዟታል።
በእርግጥ የኢፌዴሪ መንግሥት ቀደም ብሎ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ይሁን በአፍሪካ ህብረት ያበረከታቸው አስተዋፅኦዎች በአሁኑ ወቅት ለተመዘገበው የዲፕሎማሲ ድል መሠረት ናቸው።
የኢትዮጵያ መንግሥት በየትኛውም አገር ውስጥ ሠላም እንዲሰፍን የተጫወተው ሚና የሚመነጨው ሌሎች ኃይሎች በተሳሳተ መንገድ እንደሚተረጉሙት ሳይሆን የአጎራባቾች ሠላም ለአገሪቱ የልማት፣ የሠላምና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባህል ግንባታ መፋጠን ካለው ጠቀሜታ አንጻር ነው። ይህም ካለምክንያት የተፈፀመ ጉዳይ አይደለም። ድህነትና ኋላ ቀርነትን ለመዋጋት የሚደረገው ጥረት የሚሳካው ጐረቤቶች ሠላም ሲሆኑ ነው።
በእርግጥም የድንበር አዋሳኞች ቀርቶ የሩቅ አገራት ሠላም መሆን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለኢትዮጵያ ሠላም መጐልበት ያለው ሚና የጎላ እውነታ ነው። ይህም ሁኔታ በአፍሪካ ደረጃ በጋራ ሠላም እጅ ለእጅ ተያይዞ ለማደግና አፍሪካዊ ህዳሴን ማጎልበቱ አይቀሬ ይሆናል።
ያም ሆነ ይህ ኢትዮጵያ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን አማፅያን መካከል የተካሄደው ዘግናኝ ግጭት በሠላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ትልቁን ድርሻ ተጫውታ ለች። የኢትዮጵያ መንግሥት ያለውን ጠንካራ እምነት የገለፀበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህም ኢትዮጵያ የተጎናፀ ፈችው ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ ድሏ ነው።
ደቡብ ሱዳን የራሷን ነፃ አገር ከመሠረተችበት አንስቶ ኢትዮጵያ ከአዲሲቷ አገር ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ ያተኮረ ነው። ይህም በንግድ፣ በመሠረተ ልማት፣ በኢንቨ ስትመንትና በፀጥታ ጉዳዮች ላይ አተኩሯል። ምንም እንኳን በውስጥ ግጭቶች ምክንያት ሠላሟ ተመልሶ ቢናጋም።
አዲሲቷ አገር ደቡብ ሱዳን ነፃ ከወጣችበት ጊዜ አንስቶ በውስጧ የተፈጠ ረውን የእርስ በርስ ግጭት የኢፌዴሪ መንግሥት ከኢ ጋድ ጋር በመሆን አሁን ድረስ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው። በዚህም መልካም ሊባል የሚችሉ ውጤቶች ተገኝተዋል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀንድ አገራት ጋር ያላት መልካም ግንኙነት ቀጣናውን በልማት ለማስተሳሰር የምታደርገውን ጥረት እንደሚያጎለብት ተስፋ ተጥሎበታል። ይህም አንዱ የዲፕሎማሲው ከፍታ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከጐረቤት አገሮች ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት የመፍጠር ጥረት በዚህ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ አስተማማኝ ሠላምን ለማስፈን በሚካሄድ እንቅስቃሴ ውስጥ አገሪቱ ለጀመረችው የፈጣን ልማት ቀጣይነት መረጋገጥ ብቸኛው አማራጭ በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል።
ይህን ሁኔታ መነሻ በማድረግ ብሎም መንግሥት ለሠላም ካለው ጽኑ አቋም በመነሳት ለዘመናት የእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ ለቆየችው ጐረቤት አገር ሱዳን በተለይ ደግሞ በቅርቡ ሠላሟ እየደፈረሰ ለምትገኘው ደቡብ ሱዳን ሠላም መስፈን ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው።
ለዘመናት በአንድ ድርጅት ጥላ ሥር ሆነው ለሕዝባቸው ነጻነትና እኩል ተጠቃሚነት ሲታገሉ ቆይተው፣ የናፈቁትን ሠላምና ልማት በቅጡ ሳያጣጥሙ ወደ ግጭት የገቡት የደቡብ ሱዳን ሕዝቦች ዳግም ወደ እርስ በርስ ጦርነት በመግባት ለከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጥፋት መዳረጋቸው ዛሬ ድረስ የቀጠለ እውነታ ነው።
በእርግጥ በደቡብ ሱዳን የተከሰተው ወቅታዊ ችግር የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት በከፍተኛ ሁኔታ ስቧል። ይሁንና በተጨባጭ ሲታይ እንደ ኢፌዴሪ መንግሥትና ኢጋድን ያህል የበለጠ ጥረት ያደረ ማግኘት ይከብዳል።
ሁሉም እንደሚረዳው አዲሷ አገር በሆነችው ደቡብ ሱዳን የተከሰተው ቀውስ የአደጋው ተጋላጭ የሚያደርገው በዋነኛነት ዜጎቿን መሆኑን እስካሁን ከደረሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ መገንዘብ ከበቂ በላይ ማሣያ ነው። ያም ሆኖ ግን ዳፋው ለአካባቢው አገራት ጭምር መሆኑም አልቀረም።
ያም ሆኖ ይህ የኢፌዴሪ መንግሥት የቀጣናው ሕዝቦች ሠላም መሆን ቀናዒ ፍላጎት አለው። በቀጣናው ውስጥ የአንድ አገር ሕዝብ መጎዳት ዞሮ…ዞሮ ለኢትዮጵያ የሚኖረው አሉታዊ ተጽእኖ እንዳለው ይታወቃል። በመሆኑም ሕዝቦች አገራቸው ውስጥ በሠላም እየኖሩ ለቀጣናው ልማት እመርታ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ መንግሥት ያግዛል። በሂደትም ክፍለ አህጉራዊው የምጣኔ ሀብት ትስስር ይበልጥ እንዲዳብር ይበልጥ ጠንክሮ ይሰራል።

አባ መላኩ

 

 

 

Published in ፖለቲካ

የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እንደሌሎች ዘርፎች የሰለጠነና ብቃት ያለው ባለሙያ ይፈልጋል፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ የሰለጠነ እና ብቃት ያለው የሰው ሀይል እጥረት ዘርፉን እየተፈታተነ ነው፡፡ይህም ኢንዱስትሪው የሚፈለገውን እመርታ እንዳያስመዘግብ ማድረጉን ‹‹የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ተግዳሮቶች እና ምቹ ሁኔታዎች›› በሚል ርዕስ በጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህር ተካበ ስንታየሁ የተደረገ ጥናት ያመላክታል፡፡
ከሶስት ዓመት በፊት የሆቴል እና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስትቲዩት ያደረገው ጥናት እንደሚያሳየው በዘርፉ ከተሰማሩት ባለሙያዎች 23 በመቶ ብቻ ከዘርፉ ጋር ተዛማጅነት ያለው ስለጠና ወስደዋል፡፡ የተቀሩት ከዘርፉ ጋር ተዛማጅነት ያለው ስልጠናዎችን ያልወሰዱ ናቸው፡፡ ከአኃዙ መረዳት እንደሚቻለው በዘርፉ የተሰማራው አብዛኛው የሰው ኃይል ተዛማጅነት ያለው ስልጠና ሳይወስድ ነው፡፡
የሰው ሀይል እጥረትን ለመቅረፍ ብሎም ብቁ የሰው ሀይል ለማፍራት የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ተማሪዎችን ተቀብሎ በማሰልጠን ላይ ይገኛል፡፡ ለሰልጣኞቹ የንድፈ ሀሳብ ትምህርት ከመስጠት ባሻገር የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎችን እንዲጎበኙም ያደርጋል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ የሆቴል እና ቱሪዝም ተማሪዎችን በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ የመስህብ ሥፍራዎችን አስጎብኝቷል፡፡
በጉብኝቱ ተሳታፊ ከነበሩት ተማሪዎች መካከል በኢንስትቲዩቱ የሁለተኛ ዓመት የቱሪዝም ማኔጅመንት ተማሪ ዘሪሁን ዓለማየሁ አንዱ ነው፡፡ ሀገሪቱ ከአብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት የሚሻል የቱሪስት መስህቦች ባለቤት ብትሆንም በዘርፉ በሚስተዋሉ ችግሮች ሳቢያ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እያገኘች አይደለም፡፡ ጥቂት ቅርስ ያላቸው የአፍሪካ ሀገራት ከኢትዮጵያ በተሻለ መልኩ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ ይህም ሁሌም ቁጭት እንደሚፈጥርበት ነው የተናገረው፡፡
የመሰረተ ልማት እጥረት እና የመስህብ ቦታዎችን የማስተዋወቅ ችግር ሀገሪቱ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዳትሆን ማድረጋቸውን ተማሪ ዘሪሁን ይገልፃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በዘርፉ የተሰማሩት ሰዎች ተዛማጅነት ያለው ስልጠና ያልወሰዱ መሆናቸው የራሱን አሉታዊ አስተዋጽኦ አበርክቷል ይላል፡፡
በአስጎብኚነት ከሚሰሩት አብዛኛዎቹ በልምድ ወደ አስጎብኚነት የገቡ በመሆናቸው ሥራውን በአግባቡ በመወጣት ረገድ ከፍተኛ ክፍተት አለባቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ለቱሪስቱ የሚፈለገውን አገልግሎት ለመስጠት ይቸገራሉ፡፡ አዳዲስ የቱሪዝም ባለሙያዎችን ለማሰልጠን ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ለጊዜው የነባሮቹን አቅም የሚያሳድጉ ስልጠናዎች ቢሰጡ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ተናግሯል፡፡
በዘርፉ ለመስራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ እና የዘርፉ ችግሮች ባለመቀረፋቸው በርካታ ምሩቃን ሆቴሎች ውስጥ ብቻ ተቀጥረው ለመስራት እየተገደዱ ናቸው፡፡ ይህም እንደ ሀገር ሲታይ ብክነት መሆኑን ተማሪ ዘሪሁን አስረድቷል፡፡ በኢንስቲትዩቱ የተዘጋጀው ጉብኝት በመዲናዋ እና አካባቢው ስላሉ መስህቦች ያለውን እውቀት ለማሳደግና በቀጣይ መስህቦቹን ለዓለም ለማስተዋወቅ የሚያስችል ስንቅ ያገኘበት እንደሆነ አመልክቷል፡፡
‹‹በዘርፉ ያለውን ችግሮች ለመቅረፍ መንግስትና ህዝብ ተባብረው የቱሪዝም መሰረተ ልማትን በመዘርጋትና በማስተዋወቅ ረገድ ብዙ ስራ መሰራት አለባቸው፡፡ ሀገሪቱ ያሰለጠነቻቸው ውስን ባለሙያዎች በሰለጠኑበት ዘርፍ ሳይሰሩ እየባከኑ ናቸው›› ያለው ተማሪ ዘሪሁን እንደ ግለሰብ ራሱን አብቅቶ ሀገሩን ለሌላው ዓለም ለማስተዋወቅ መዘጋጀቱን ይናገራል፡፡ ሀገሩን ወክሎ በውጭ ዜጎች ፊት የሚቆም ሰው እንደመሆኑ ራሱን ለማብቃት ትኩረት ሰጥቶ ስልጠናውን እየተከታተለ መሆኑን ነው ያብራረው፡፡ ባገኘው መድረክ ሁሉ ሀገሩን ለማስተዋወቅ ተዘጋጅቷል፡፡ መስህቦችን መጎበኘት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ይናገራል፡፡
ተማሪ ነጃት ሚፍታህ ደግሞ በኢንስቲትዩቱ የአንደኛ ዓመት ተማሪ ስትሆን የጉብኝቱም ተሳታፊ ነች፡፡ ጉብኝቱ ተማሪዎች የት ሄደው፣ ምን ማድረግና ምን መናገር እንዳለባቸው እንዲያውቁ ይረዳል፡፡ በሀገሪቱ ያሉትን ቅርሶች የማወቅና የማስተዋወቅ እድል እንደሚፈጥርላት ገልፃለች፡፡
ጉብኝቱ የተለየ ስሜት እንደፈጠረባት ተናግራ፤ ስለ ቦታዎቹ በታሪክ ከመስማት ባለፈ በቦታው ተገኝታ የማየት እድል ማግኘቷ አስደስቷታል፡፡ በመስህብ አካባቢዎቹ የእንክብካቤ ማነስ እንዳለ ታዝባለች፡፡ ይህን ማስተካከል እንደሚገባ ጠቁማ ቅርሶቹና የመስህብ ሥፍራዎቹ ታሪካዊ ይዘታቸውን ይዘው መታደስ እንዳለባቸው አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አሸብር ተክሌ በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ የመጀመሪያው የሆቴል እና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ተቋም የሆነው ኢንስቲትዩቱ በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፎች በርካታ ባለሙያዎችን ማሰልጠኑን ይገልፃሉ፡፡ ባለሙያዎቹም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት በትላልቅ ሆቴሎች ፣ሬስቶራንቶች እንዲሁም በቱሪዝም ድርጅቶች ውስጥ በመስራት ራሳቸውን እና ሀገራቸውን በመጥቀም ላይ ናቸው ብለዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ስልጠናውን ከሆቴል እና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ጋር በቅንጅት ይሰጣል፡፡ ኢንስቲትዩቱ የሚሰጠው ስልጠና 30 በመቶ ንድፈ ሀሳብ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ሲሆን 70 በመቶው የተግባር ነው፡፡ ሆኖም በዘርፉ አሁንም የሰለጠነ የሰው ሀይል እጥረት ይስተዋላል፡፡ የሰለጠነ የሰው ሀይል እጥረት ችግርን ለመቅረፍ የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ አስቀምጧል፡፡ በፍኖተ ካርታው ከተቀመጡት ነጥቦች አንዱ ስልጠናን በክልሎች ተደራሽ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ከፌዴራል የቴክኒክና ሙያ ኤጀንሲ እና ከክልል ቴክኒክና ሙያ ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት በክልሎች 11 የሚደርሱ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ስልጠና የሚሰጡ ቅርጫፍ ተቋማት የተለያዩ ስልጠናዎችን የሚሰጡበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡
ማሰልጠኛዎችን ተደራሽ ለማድረግ በየክልሉ ክላስተር ማዕከላት ተቋቁመው የማሰልጠን ስራ ተጀምሯል፡፡ ይህተጠናክሮ እንዲሄድ አካባቢውን የሚያውቅ እና በትክክል ሊያስጎበኝ የሚችል፣ ሀገሩንና የሀገሩን ቅርስ የሚወድ እና የሚንከባከብ ዜጋ የማፍራት ስራውን ኢንስትቲዩቱ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ አሸብር ገልጸዋል፡፡
ሰልጣኞቹ ገንዘብ አግኝቼበታለሁ በሚል ብቻ ሳይሆን በዘርፉ መስራት የሚያስከፍለውን መስዋዕትነት ጭምር አውቀው የሚያጋ ጥሟቸውን ችግሮች ለመቋቋም ስነ ልቦናዊ ዝግጅት እንዲያደርጉ እየተሰራ ነው፡፡ በተለይም ሰልጣኞቹ በስነ ምግባር እንዲታነጹ ማድረግ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ በመሆኑ አስጎብኚዎቹ ራሳቸውን አብቅተው የጎብኚዎችን ፍላጎት ቀድመው ተረድተው አገልግሎት ለመስጠት ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ እየተደረገ መሆኑን አቶ አሸብር ተናግረዋል፡፡
ሰሞኑን የተደረገው ጉብኝትም የቱሪዝም ባለሙያዎች የሀገራቸውን አጠቃላይ ገጽታ እንዲገነዘቡ፣ አካባቢያቸውን በአግባቡ እንዲያውቁና ያሉትን ቅርሶች ምንነት እና ታሪክ እንዲገነዘቡ ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነ ተመልክቷል፡፡
ጉብኝቱ ተማሪዎች በአግባቡ እንዲያውቁና ያወቁትንም ለሌሎች እንዲያሳውቁ ግብዓት ይሆናቸዋል፡፡ ጉብኝቱ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይወሰን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎችም እየተደረገ ነው፡፡ ተማሪዎች እያንዳንዱን የቱሪስት መዳረሻ ከጥንተ መሰረቱ ታሪኩን አውቀውና ተረድተው ለጎብኚዎች የሚያስተላልፉበትን እድል እንደሚፈጥር ተነግሯል፡፡
‹‹ሀገሪቱ የበርካታ ቅርሶች ባለቤት ናት›› የሚሉት አቶ አሸብር ይህንን ቅርስ ለዓለም ለማሳወቅ እና ከዛም ትውልዱ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ስራ እየፈጠረ እነዚህን ቅርሶች በአግባቡ ለዓለም ካስተዋወቀ ተጠቃሚ የሚሆንበት ዕድል ሰፊ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም ሁኔታዎች እየተመቻቸ ሲሆን ፤ጉብኝቱም የዚሁ አንድ አካል መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አቶ አሸብር እንደሚሉት ከ300 በላይ ሰልጣኞች የተሳተፉበት ጉብኝት አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን ተማሪዎቹ በአግበቡ እንዲያውቁ የሚያስችላቸው ነው፡፡ የተደረገው ጉብኝት ሰልጣኞቹ በቀጣይ ራሳቸውን ችለው ወደ ኢንዱስትሪው ሲቀላቀሉ ዘርፉን በማስተዋወቅ እና በሁነት ዝግጅት ላይ እንዴት መስራት እንዳለባቸው ተግባራዊ ልምድ እየቀሰሙ የሚሄዱበትን ሁኔታ ፈጥሯል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ቀደምት አባቶች ያስቀመ ጧቸው የታሪክ አሻራዎች ምን እንደሚመስሉ ተማሪዎቹ እንዲያውቁ፤ አባቶች ለሀገሪቱ ሉዓላዊነት የከፈሉትን መስዋዕትነት የሚገልፁ በየሀውልቱ ላይ የተፃፉ ታሪኮችን እንዲገነዘቡ፤ አባቶች ምን ያህል መስዋዕትነት ከፍለው ሀገሪቷን እንዳቆዩዋት እንዲረዱ፤ ነገ ተመርቀው ኢንዱስትሪውን ሲቀላቀሉ ደግሞ ታክን እንዲያስረዱ፤ ትውልዱ ምን እንደሚጠበቅበት አውቆ ለሀገሩ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት በማድረግ ረገድ ጉብኝቱ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡
እንደ አቶ አሸብር ማብራሪያ በተለይ የቱሪዝም ትምህርት ክፍል ሰልጣኞች በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እየጎበኙ ተግባራዊ ልምድ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፡፡ የሆቴል ተማሪዎች ደግሞ ሆቴል እየገቡ በእንግዳ አቀባበል፣ በምግብ ዝግጅት፣ በቤት አያያዝ ዙርያ የሆቴሎች አሰራር ምን ይመስላል የሚሉትን? የሚያዩበት እድል እየተመቻቸ ነው፡፡
ተማሪዎች ወደ ፊት የሚሰሩትን ስራ በአግባቡ ማየታቸው ነገሮችን እንዲገነዘቡት እድል ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ሲያዩ ምን አይነት አወቃቀር አለው? በቦታው ያሉ ታሪካዊ ነገሮች ምንድን ናቸው? እንዴት ተሰራ? የሚሉትን ለመረዳት እና በዘመኑ የነበሩ ሰዎች ቅርሱን ለመስራት የነበራቸውን ትጋት እና ችሎታ ለማወቅ ይረዳል፡፡ ይህ መሆኑ ያዩትን ለሌላ ሰው ለማስረዳት አይፈሩም፣ አይሸማቀቁም፡፡ ነገ አስጎብኚ ሆነው ሲወጡ በልበ ሙሉነት መልዕክት ለማስተላለፍ አይቸገሩም፡፡

መላኩ ኤሮሴ

Published in ኢኮኖሚ

የምስራቅ አፍሪካዋ ሶማሊያ በርካታ ስፍራዎች በአሸባሪው ቡድን አልሻባብ ቁጥጥር ስር ከነበሩበት ጊዜ አንስቶ ለውስጧ ፖለቲካም ለጎረቤቶቿ ደህንነትም ሥጋትን አርግዛ ቆይታለች፡፡ በቀጣናውና በሌሎች አገሮች የፀረ-ሽብር ዘመቻ ጥምረት በተወሰዱ ተደጋጋሚ ጥቃቶች የሽብር ቡድኑ ተዳክሟል፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያዘናጋ የሚሰነዝራቸው ጥቃቶች የሽብር ቡድኑ ጨርሶ አለመፈራረሱን ያሳያል፡፡ ከዚህ ውጭ ሶማሊያ ከሁለት አስርት ዓመታት ቀውስ በኋላ ከሰላም የታረቀች ብትመስልም አሁን ደግሞ አሰላለፉን በቀየረ አዲስ የሽኩቻ አዙሪት ውስጥ የገባች ይመስላል፡፡
በአካባቢው መስፋፋት የጀመረው የባህረ ሰላጤው አገራት የግዛት ትንቅንቅ የባህር ዳርቻዎቹን ማራኪ ስፍራዎች የሥጋት ማዕከል አድርገውታል፡፡ የቢቢሲዋ ፀሐፊ ሜሪ ሀርፐር እንዳሰፈረችው ዘገባ፤ ስፍራው ላይ የሚካሄደው የሌሎች አገሮች እንቅስቃሴ ሶማሊያን ከሶማሊላንድ ማፋጠጥ ጀምሯል፡፡ በእርግጥ በሁለቱ ወገኖች መካከል ውጥረቱ ቢነግስም ለአጠቃላይ ቀጣናው ሥጋት መሆኑን እንደማይቀር ተንታኞች ይገልፃሉ፡፡
በዓለም አቀፍ ፖለቲካዊ ቀውሶች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ተቋም የአፍሪካ ቀጣና ፕሮጀክት ዳሬክተርና የፖለቲካ ተንታኙ ረሺድ አብዲ ‹‹ሶማሊያ በአንድ በኩል ኳታር እና ቱርክ፤ በሌላ በኩል ሳውዲ አረብያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለሚያካሂዱት የወታደራዊ ኃይል ጨዋታ ሜዳ ሆናለች›› ይላሉ፡፡ አያይዘውም ይሄ የባህረሰላጤው አገራት ፉክክር ከሶማሊላንድ ወደ መላው አፍሪካ ሊዛመት እንደሚችል ያላቸውን ሥጋት ያስቀምጣሉ፡፡
የፖለቲካ ተንታኙ እንደሚሉት፤ የአገራቱ ፍላጎት በጊዜ ሂደት መላው አፍሪካን ታላሚ ያደርጋል፡፡ ምንም እንኳን ይሄ የማይታሰብ ቢመስልም ከበርበራ ወደብ መገኛዋ ሶማሊላንድ ወደ ተጎራባቿ ሶማሊያ መዛመቱ ላይ ግን ጥርጥር የላቸውም፡፡ ለዚህ ደግሞ በተለይ ሶማሊያ ተደጋግሞ ከሚያጋጥማት የሽብር ጥቃት ጋር በተያያዘ አሁንም ፀጥታዋ በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ አለመገኘቱ ተጋላጭ ያደርጋታል፡፡ በተጨማሪም ሶማሊላንድና ሶማሊያ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር በተደረገ ስምምነት አለመግባባት ውስጥ መግባታቸው ሌላኛው ምክንያት ይሆናል፡፡
አሁን የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በበርበራ የጦር ሰፈር ገንብታለች፡፡ የቀጣናው ፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ታዲያ፤ ይሄ የጦር ሰፈር ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ፋይዳ ያለው ነው፡፡ በተመሳሳይ አሜሪካና ሩስያም በስፈራው የጦር ሰፈር ካደራጁ አስር ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ በአህጉሩ ረጅሙና እስከ አራት ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የአውሮፕላን መንደርደሪያም እዚሁ ስፍራ ይገኛል፡፡
ጥያቄውም ለመሆኑ አገራቱ ለምን በተናጠል በዚህ ስፍራ የመመስረት ፍላጎት አደረባቸው? የሚለው ይሆናል፡፡ የሶማሊላንዷ በርበራ ወደብ ፍፁም በሚመች መልኩ መረጋጋት ለናፈቃት የመን ቅርብ ናት፡፡ ይሄ ደግሞ ሳውዲ መራሹ የጦር ዘመቻ በኢራን እንደሚደገፍ በሚታመነው የሁቲ አማፅያን ላይ የተጠናከረ ጥቃት ለመሰንዘር ሁኔታውን ያመቻችለታል፡፡ ከበርበራ በተጨማሪ ኤርትራ ለተመሳሳይ አላማ የሚሆን የጦር ሰፈር በአሰብ አካባቢ ለተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መፍቀዷ ይሄንኑ አላማ ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡
ከተጠቀሰው ፖለቲካዊ አላማ ባሻገር በስፍራው ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጥቅም ማጠንጠኛ ለማድረግም የተግባር ጥረት አለ፡፡ ለአብነትም ይላሉ ተንታኞች፤ መሰረቱን በዱባይ ያደረገው ዲፒ ዎርልድ ኩባንያ ወደቡን የመቆጣጠር ከፍተኛ ፍላጎት አለው፡፡ ምክንያቱም በዚህ ወደብ ወደተቀሩት ባህረሰላጤው አገሮች በሚሊዮን የሚቆጠር የቁም እንስሳት የወጪ ንግድ ለማቀላጠፍ ያስችላል፡፡ ይሄ ደግሞ በወደቡ ላይ ድርሻ ያላት ኢትዮጵያ ለኪራይ ከፍተኛ ወጪ ከምታወጣበት የጂቡቲ ወደብ በተጨማሪ ሌላ አማራጭ የማስፋት ዕድሏ ላይ አሉታዊ አስተዋጽኦ እንዳይኖረው ያሰጋል፡፡
በእርግጥ ይሄ የሶማሊላንድ እንቅስቃሴ ሞቃዲሾን የሚያስደስት አልሆነም፡፡ ምንም እንኳን ሶማሊላንድ ሉአላዊ አገር ነኝ ብትለም አሁንም ድረስ ለሶማሊያ አይዋጥላትም፡፡ እንዲያውም በቅርቡ ዲፒ ዎርልድ ኩባንያ እና ሶማሊላንድ የፈፀሙትን የወደብ ስምምነት የሶማሊያ ፓርላማ ድምፅ ሰጥቶ ሕጋዊ እውቅና ነፍጎታል፡፡ የሶማሊያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ ኢሴ አዋድ ‹‹የሶማሊላንድና ዲፒ ዎርልድ ኩባንያ ተግባር በጣም ንቀት የተሞላበት ነው›› በማለት ከአገራቸው እውቅናና ፈቃድ ውጭ ኩባንያው ምንም አይነት ሕጋዊ ውል ማሰር እንደማይችል አሳስበዋል፡፡
ነገር ግን ዛቻ ለተሞላበት የሞቃዲሾ ቁጣ ቁብ የሰጡ የማይመስሉት ሁለቱ አካላት ለስምምነታቸው ሕጋዊ እውቅና ራሳቸው ሰጥተው ፕሮጀክታቸውን ለመቀጠል ቆርጠዋል፡፡ ሶማሊያ ከሞቃዲሾ ተሻግራ ስምምነቱን የማስተጓጎል አቅም አላት ብለው እንዳማያስቡም ሁለቱ አካላት ዕምነት አላ ቸው፡፡ ለዚህም የሶማሊ ላንድ ባለስልጣናት አቋም እንደማሳያ ይጠቅ ሱታል፡፡
በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሶማሊላንድ አምባሳደር በሼ አዊል ኦማር፤ ሶማሊያ በጉዳዩ ላይ ያሳየችው አቋምን ‹‹ማላገጥ›› በማለት ጉዳዩን አጣጥለውታ፡፡ አምባሳደሩ አያይዘውም ‹‹ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የራሳችንን ጉዳይ ስናስተዳደር በመኖ ራችን አሁን በጉዳያችን ጣልቃ ገብታ ስምምነቱን የማስተጓጎል መሰረት አይኖራትም›› ሲሉ ገልፀዋል፡፡ እንዲያ ውም ይላሉ፤ ከኩባንያው ስምምነት ባሻገር የጦር ሰፈር ግንባታው የወታደራዊ ስልጠናዎችን ስለሚያስገኝ ለሶማሊላንድ ፀጥታ መጠናከር ወሳኝ ነው፡፡
ተንታኞች እንደሚሉት፤ የሶማሊያ ሥጋት ለሶማሊላንድ እውቅና የመስጠት ያለመስጠት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁኑም የፌዴራል መንግሥቱ ሥጋት በሶማሊላንድ በኩል ጠጋ ጠጋ የጀመሩት የባህረ ሰላጤው አገራት በተለይም አረብ ኤምሬቶች ወደ ውስጥ ዘልቀው ከክልል መንግሥታት ጋር የተናጠል መስተጋብር እንዳይፈጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም ይሄ አዝማሚያ ከዓመታት በኋላ ወደመንግሥታዊ ሥርዓት ተሸጋግራ ዳዴ ማለት ለጀመረችው ሶማሊያ ጉዞ የኋሊት ይሆናል፡፡
ሶማሊያ ሥጋቱ ቢያስጨንቃት ብዙ የሚደንቅ አይሆንም፡፡ በፌዴራል መንግሥት ምስረታ ማግስት ጀምሮ የአምስቱ የክልል መንግሥታት ሁኔታ ለማዕከላዊው መንግሥት የተረጋጋ እንቅልፍ የሚሰጥ አይደለም፡፡ መንግሥታቱ እርስ በእርሳቸውም ይሁን ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር ያላቸው ግንኙነት የውሃ ቀጠነ ምክንያት ፈላጊነት እንደሆነ ይነገራል፡፡ እንዲያውም የተወሰኑት የክልል መንግሥታት ያለማዕከላዊ መንግሥቱ ፈቃድ ወታደራዊ ስልጠና፣ ትጥቅና የገንዘብ ድጋፍ ከኤምሬትስ ይቀበላሉ፡፡ ይሄ ድጋፍ ደግሞ በእጅ አዙር ከዲፒ ዎርልድ ኩባንያ የሚደጎም ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወደቡ ላይ ያለውን ማንዣበብ ከፍ አድርጎታል፡፡
ሶማሊያ በሶማሊላንድ የሚደረጉ ስምምነቶችን በንቃት እየተከታተለች ‹‹አላምንበትም›› ብትልም በሞቃዲሾና አካባቢውም የቱርክ ተፅእኖ መስፋት ጀምሯል፡፡ በአካባቢው የቱርክ የጦር ኃይል ከፍተኛ ስፍራን የተቆጣጠረ ልምምድ ቦታ አለው፡፡ በተጨማሪም ሁለቱ አገራት በጋራ የሚያስተዳደሩት ወደብ በቱርኩ ኩባንያ አልባይራክ እየተዳደረ ይገኛል፡፡
ሶማሊያ አሁን በአካባቢው የተለያዩ አገሮች የጥቅም ፍላጎት ማዕከል መሆኑ ማዕከላዊውን መንግሥት ያሳሰበው ይመስላል፡፡ ምንም እንኳን ለቱርክና ኳታር ታማኝነቱን ቢያሳይም በሶማሊላንድ በኩል ሳውዲና አረብ ኤምሬቶች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በአካባቢው የለየለት መከፋፈልን እንዳያመጣ ያሰጋል፡፡ ይሄ ደግሞ ከፖለቲካ ሥጋት ባሻገር በሶማሊያ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ይኖረዋል፡፡ ምክንያቱም የሶማሊያ 80 በመቶ የቁም እንስሳት ተረካቢ ሳውዲ ናት፡፡ አጋሯ ኳታር ከምትረከባት ሦስት ነጥብ አምስት በመቶ ብቻ ነው፡፡
ሶማሊላንድ እ.ኤ.አ 1991 ጀምሮ ራሷን እንደ ሉአላዊ አገር አድርጋ ብታውጅም የምትፈልገውን ያህል እውቅና አልተቸራትም፡፡ ነገር ግን በአንፃራዊነት ስትታይ በፖለቲካዊ መረጋጋት በኩል ከሶማሊያ የተሻለች መሆኗ ይነገራል፡፡ ምክንያቱም ሶማሊያ አሁንም ድረስ እያዘናጋ ጥቃት በሚፈፅመው የሽብር ቡድን ጥቃት ሙሉ ለሙሉ ነፃ አልወጣችም፡፡ እንዲያውም የሽብር ቡድኑ ከቅርበ ጊዜ ወዲህ የጥቃት ኢላማውን ወደ ባለሥልጣናትና መንግሥታዊ ቢሮዎች ማዞሩ ይነገራል፡፡ ይሄም የማዕከላዊ መንግሥቱን ለማዳከም በማሰብ መሆኑ ይገመታል፡፡
አሁን የሶማሊያ ፍላጎት በባህረሰላጤው አገራቱ መካከል የተጀመረው ለቀውስ ያመዘነ ፉክክር ውስጥ እጇን ላለማስገባት ነው፡፡ ነገር ግን ለአገራቱ ግብግብ ፈረስና ሜዳ ሰጥቶ ‹‹ከደሙ ንፁህ ነኝ›› ማለት ለብዙዎች የሚዋጣ አይመስልም፡፡ የቢቢሲ የአፍሪካ ቀንድ ተንታኙ አሌክስ ዲዋል፤ ሶማሊያ ገለልተኛ ለመሆን ብትጥርም የቀጣናው አዝማሚያ ድንበር ሊሻገር ይችላል ባይ ነው፡፡ ሽኩቻው እንዲህ ከቀጠለ ደግሞ ግብፅን ጨምሮ የተለያዩ አረብ አገራት በአካባቢው ላይ ያሻቸውን ፖለቲካዊ ጫና ለመፍጠር ጥረት ማድረጋቸው አይቀርም፡፡

ብሩክ በርሄ

Published in ዓለም አቀፍ
Thursday, 10 May 2018 19:30

ዲፕሎማሲያዊ ስኬት

ዲፕሎማሲ በዓለምአቀፉ ፖለቲካ ውስጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡በተለያዩ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ሥርዓቶች ውስጥ ከፍተኛ ፉክክር እሽቅድምድም የውጭና የውስጥ ትግል ትንቅንቅ አለ፡፡ የሚፈጠሩ የጥቅም ግጭቶችና ተቃርኖዎች፤ የፖለቲካና ኢኮኖሚ፣ የወታደራዊ ኃይልና የቴክኖሎጂ ፍጥጫ በከረረ መልኩ እንዲከሰት ያደርጋሉ፡፡ በአካባቢያዊና አህጉራዊ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ወሳኝ ለመሆን የበላይነትን ለማስከበር የሚደረግ ታላቅ ትንቅንቅ ባለበት ዘመን ላይ ነው ስለሆነም ዲፕሎማሲ ብርቱና ወሳኝ የራስን ሚዛን ማስጠበቂያ መሣሪያ ነው፡፡
ዓለማችን በሰላም አብሮ የመኖር፣ የመከባበርና የመቻቻል ዲፕሎማሲን መከተል ካልቻለች መጪው ዘመን የጦርነትና የግጭት እንዳይሆን በብርቱ ያሰጋል፡፡ ኃያላኑ መንግሥታት የተጽእኖ አድማሳቸውን ለማስፋት በኢኮኖሚና በፖለቲካው የበላይ ሆነው ለመቀጠል በሚያደርጉት ፉክክር በወሳኝነት የሚጠቀሙበት መንገድ ዲፕሎማሲ ነው፡፡ በሁሉም መስክ በሀገራት መካከል ለሚነሱ የተለያዩ ችግሮች መፍቻው የበለጠ መግባባት መፍጠሪያውም መንገድ ዲፕሎማሲ ነው፡፡
በሀገራት መካከል የሚፈጠሩ የድንበርም ሆነ የጥቅም ግጭቶችን እንዲሁም ወደጦርነት ሊያመሩ የሚችሉ የልዩነት መካረሮችን ማስወገጃው ማሸማገያው ወደ ድርድር ጠረጴዛ መሳቢያው መንገድ ዲፕሎማሲ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ብሔራዊ ጥቅሟን ያስከበሩ ለዚህም ጥግ ድረስ ሄደው ሲሟገቱ የነበሩ ብልህና አርቆ አሳቢ ዲፕሎማቶች የነበሯትና ያሏት ሀገር ነች፡፡ የዛሬው ሀገራዊ የዲፕሎማሲ መርሀችንም ኢትዮጵያ ለሁሉም ወዳጅ ናት ለማንም ጠላት አይደለችም የሚል ነው፡፡ ከጎረቤቶቻችንም ሆነ ከዓለም ጋር ያለን ግንኙነት በወዳጅነት በወንድማማችነት፣ በሰላም በጉርብትና አብሮ በመኖር መርህ የተቃኘ ነው፡፡
የሰሞኑ የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ የጎረቤት ሀገራት ጉብኝት ከሀገራቱ ጋር የነበረንን ግንኙነት በአዲስ ተስፋና መንፈስ እንዲታደስ ያደረገ ነው፡፡ ጎረቤቶቻችን ተፈጥሮባቸው የነበረውን ኢትዮጵያ ወዴት እየሄደች ነው? ተዳክማለች፣ ተከፋፍላለች የሚለውን የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲጠራ አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሮቿን በራሷ የመፍታት አቅም ያላት ታላቅ ሀገር መሆኗን ለጎረቤቶቿም ሆነ ለዓለም አሳይታለች፡፡ በዲፕሎማሲው መስክ ጠንክራ በመውጣት የተለመደ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ማዕከልነቷን ቀጥላለች፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ በጅቡቲ፣ በሱዳንና በኬንያ ያደረጉት ጉብኝት የተሳካ ነው፡፡ ከጎረቤቶበ ቻችን ጋር በጋራ አብረን እንደምንኖር ሁሉ በኢኮኖሚ ተሳስርን ተጋግዘን ለማደግ እንደምንችል ያሳየም ነው፡፡ የቀድሞውን ትብ ብር ያጎለበተና አዳዲስ የትብብር ምዕራፎችን ከፍቷል፡፡ ይህም ለኢት ዮጵያ ታላቅ ዲፕሎ ማሲያዊ ስኬት ነው፡፡ ዛሬም የዳበረ የኢኮኖሚ አቅም የገነባች በምሥራቅ አፍሪካም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ተሰሚነትና ተደማ ጭነት ያላት ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር መሆኗን ዳግም አስመስክራለች፡፡
ኢትዮጵያ በዲፕሎማቲክ መስኩ የአፍሪካ ሕብረት መስራችና ዋና ጽሕፈት ቤት ከምስረታው እስከዛሬ የሚገኝባት ናት፡፡ ለአፍሪካ ነፃነት ታላቅ ተጋድሎ ያደረገችና በአቅሟ ያገዘች ነች፡፡ አፓርታይድንና ዘረኝነትን ስትዋጋ ኖራለች፡፡ የደቡብ አፍሪካውን ኔልሰን ማንዴላ ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ የነፃነት ተዋጊዎችን ረድታለች፡፡ አሰልጥናለች፡፡
በአፍሪካ ዲፕሎማሲ ውስጥ ትናንትም ዛሬም ከፍተኛ ተጽእኖ አሳዳሪና የላቀ ስፍራ ያላት ሀገር ናት፡፡ በተከታታይ ዓመታት ባስመዘገበችው የኢኮኖሚ ስኬት የገነባችው ብሔራዊ ኢኮኖሚ በቅርቡ አይ.ኤም.ኤፍ ባወጣው መረጃ መሠረት በአፍሪካ በኢኮኖሚውም የመሪነት ቦታ ለመረከብ አስችሏታል፡፡
በሀገራዊ ቀውስ ውስጥ በነበርንበት ወቅት የኢንዱስትሪና የማኑፋክቸሪንግ የሌሎችም ዘርፍ እድገቶቻችን አልተገቱም፡፡ በሙሉ ሀገራዊ ሰላም ስንሰራ ደግሞ ምን ያህል ከፍ ብለን እንደምናድግ መገመት ይቻላል፡፡ በዲፕሎማሲው መስክ ተደማጭ ለመሆን ከፍተኛ ብሔራዊ አቅም መገንባትን ይጠይቃል፡፡
በዲፕሎማሲው መስክ ተጽእኖ አሳዳሪ ከሆነው ሁኔታ ውስጥ ጠንካራ ብሔራዊ የመከላከያ ኃይል፣ ሀገራዊ ሰላምና የተረጋገጠ ደህንነት መኖሩ ወሳኝ ነው፡፡
በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ ነን፡፡ እንደገናም በመከላከያ ኃይላችን ዘመናዊ አደረጃጀትና ጥንካሬ በአፍሪካ በሁለተኛነት ደረጃ እንገኛለን፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ግዳጅ ሁልጊዜም በብቃቱና በዲሲፕሊኑ ተመራጭ የሆነ ከራሱ ሀገር አልፎ ለሌሎች ሀገራት ሰላም መከበር የሚቆም ሠራዊት ባለቤቶች ነን፡፡ ይህም በአካባቢና በዓለም አቀፉ ዲፕሎማሲ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ እንዲኖረን ያደርጋል፡፡
የጎረቤት ሀገራት ሰላም የራሳችን ሰላም ነው፡፡ የጎረቤት ሀገራት ማደግና መበልጸግ የራሳችን ማደግና መበልጸግ ነው በሚለው ቀና የዲፕሎማሲ ስሌት መራመድ ወዳጅነትን ማጎልበት ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ በሀገራችን ባሕልም ሰላም አውለኝ ሰላም አሳድረኝ ከነቤቴ ከነጎረቤቴ ይባላል፡፡ጎረቤትም ሆነ ጎረቤት ሀገር ሰላም ካልሆነ ችግሩ ለሌላው ጎረቤት ይተርፋል፡፡የብቻ ሰላም አይኖርም፡፡ ጎረቤታችን በሆኑት ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ሲካሄድ የነበረው ጦርነትና ግጭት መዘዙ ለእኛም ተርፏል፡፡ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጦርነትን በመሸሽ ተሰደው የገቡት ወደ ኢትዮጵያ ነው፡፡ ግጭቱና እልቂቱ ሲበዛ የሚሰደዱት ቅርብ ወደሆነ ጎረቤት ሀገር ነው፡፡
የጦርነቱ የሰደድ እሳት ወደእኛ እንዳያልፍ ከመከላከል አልፈን በጉርብትናችን እንደገና የእነሱን ሰላም ለማረጋጋት ለማስከበር የገባንበት አሁንም ያለንባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ በዲፕሎማሲው ዓይን ሲታይ ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ኢትዮጵያ እየተጫወተችው ያለው ሚና የጎላ ነው፡፡
በብዙ መቶ ሺህ ስደተኞች ከደቡብ ሱዳን ብቻ ጦርነቱን ፈርተው ተሰደው ሀገራችን ሲገቡ ተቀብለናል፡፡ አሁንም አሉ፡፡ በኤርትራ ውስጥ ባለው የውስጥ ችግር ብዙ ሺህ ሰዎች ተሰደው ድንበር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል፡፡ ዛሬም አሉ፡፡ በአጭሩ በዙሪያችን ባሉ ጎረቤት ሀገራት የሚኖረው ሰላም የእኛም ሰላም ነው የምንልበት ምክንያት ይሄው ነው፡፡
በዚህ ጽሑፍ መግቢያ ላይ ባሉ አንቀፆች እንደተብራራው የዲፕሎማሲ ዋናው ግብ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር ነው፡፡ ከሀገር በፊት የሚቀድም ጥቅም የለም፡፡ ጎረቤቶቻችን ሆነ ሌሎች ሀገራት የራሳቸውን ብሔራዊ ጥቅም በማስቀደም ለዚህም ተግተውና ጠንክረው ይሰራሉ፡፡ ስለሆነም የእኛ አካባቢያዊም ሆነ ዓለም አቀፍ ተደማጭነትና ተጽእኖ ፈጣሪነት እያደገ ከሚጎለብተው ኢኮኖሚያችንና የዲፕሎማሲ ብቃታችን ጋር ተቆራኝቶ መራመድ ግድ ይለዋል፡፡ ለዚህም እውን መሆን ያለመታከት መስራት ይጠበቅብናል፡፡ ሀገራዊ መከበርና መታፈርን የሚያስገኘው ሰርቶ በማደግና በመለወጥ የላቀ ኢኮኖሚን በመገንባት ብቻ ነው፡፡ ዲፕሎማሲው በዚህ ይታጀባል፡፡ በዲፕሎማሲው መስክ ያለንን ክብርና ተደማጭነትም በስኬት ይዘን እንቀጥላለን፡፡

መሐመድ አማን 

Published in አጀንዳ

የኢትዮጵያና ኤርትራ የድንበር ግጭት የተጀመረበት ሃያኛ ዓመት ላይ እንገኛለን፡፡ የኤርትራ መንግሥት በታንክ የታገዘ ሠራዊት በአካባቢው የነበሩ ሚሊሻዎችና ፖሊሶችን በማጥቃት ባድመን የተቆጣጠረው ግንቦት 4 ቀን 1990 ዓ.ም ነው፡፡ ይህ ወረራ ከተፈጸመበት ቀን ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ቅድሚያ ለሰላም በመስጠት ችግሩን በውይይት ለመፍታት የሰላም እጃቸውን ዘርግተው ነበር፤ ተቀባይ አላገኘም እንጂ፡፡
መጀመሪያ በሩዋንዳ መንግሥት፤ ቀጥሎም በአሜሪካ መንግሥት እንዲሁም ሌሎች ወገኖች ችግሩን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የኤርትራ መንግሥት በወረራ ከያዛቸው አካባቢዎች ለቅቆ እንዲወጣ ቢጠየቅም ጆሮ ዳባ ልበስ በማለቱ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የሰላም ጥሪዎች ከሽፈዋል፡፡ በመሆኑም ሁለት ዓመት የፈጀ ጦርነት ተካሂዶ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን አስከብራለች፡፡
ከጦርነቱ ማብቃት ማግስትም የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ነገሮች ወደነበሩበት ይመለሱ ዘንድ የሰላም እጃቸውን ከመዘርጋት አልተቆጠቡም፡፡ዛሬም ድረስ ለሰላም ያላቸው አቋም አልተለወጠም፡፡
የሁለቱ ሀገር ሕዝቦች በባህል፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋና ሥነ ልቦና አንድ በመሆናቸው በጋራ ማደግና ከድህነት መውጣት የሚችሉበት ዕድል ሰፊ መኖሩን የተገነዘቡት የሀገራችን መንግሥትና ሕዝብ እጃቸውን ለሰላም ከዘረጉበት ወቅት አንስቶ እስከአሁን ድረስ ስለሰላምና በጋራ አብሮ ስለማደግ ሲሉ የዘረጉት እጅ አልታጠፈም፡፡ በኤርትራ በኩል ግን አሁንም ግትር አቋም በያዘ ሥርዓት ምክንያት እንኳን በራሱ ተነሳሽነት ሰላም ሊፈጥር ቀርቶ የቀረበለትን ሰላም መቀበል አልቻለም፡፡ ይህ አቋሙ በዋናነት የኤርትራ ሕዝብን ዋጋ ያስከፈለ ቢሆንም ለኢትዮጵያና ለአካባቢው ሀገሮች ከመልካም ጉርብትና ይገኝ የነበረውን ጥቅምም አሳጥቷል፡፡ ስለሆነም ዛሬም የሰላም ጥሪ ይቀበል ዘንድ እናሳስባለን፡፡
ከታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ጀምሮ እስከ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ድረስ ለኤርትራ መንግሥት የሰላም ጥሪ ቀርቧል፡፡የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ለሰላም ሲባል አስመራ ድረስ ሄደው ለመወያየት ዝግጁ መሆናቸውን መግለጻቸውም ይታወሳል፡፡ ይህም የሚያሳው የኢትዮጵያ መሪዎች ለሰላም ያላቸውን የማይናወጥ አቋም ነው፡፡በኤርትራ በኩል ያለው አመራርና ሥርዓት ግን አሁንም በግትር አቋሙ በመጽናቱ ሁለቱ ሕዝቦችና ሀገራት ከሰላም ሊያገኙት የሚገባ ጥቅም ማግኘት ሳይችሉ ሃያ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህ ነባራዊ ሁኔታ መለወጥ አለበት፡፡
ለሰላምና ለመልካም ጉርብትና ዋጋ የሚሰጥ አስተሳሰብ በኤርትራውያን በኩል መምጣት ይኖርበታል፡፡ ችግሮችንና ልዩነቶችን በውይይትና በሰጥቶ መቀብል መርህ መፍታት እየተቻለ የሁለቱን ሀገሮች ሕዝቦች ከሰላምና ከመልካም ጉርብትና ተጠቃሚነት ማራቅ ተገቢ አይደለም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ በበዓለ ሲመታቸው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባደረጉት ንግግር «ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለዓመታት ሰፍኖ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃም ከልብ እንፈልጋለን። የበኩላችንንም እንወጣለን፡፡ በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለቱ ሀገር ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል ልዩነቶቻችንን በውይይት ለመፍታት ያለንን ዝግጁነት እየገለፅኩ የኤርትራ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም እንዲወስድ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ» ሲሉ መግለጻቸው አሁንም በኢትዮጵያ በኩል ለሰላም የተዘረጋው እጅ አለመታጠፉን ማረጋገጫ ነው፡፡ ስለዚህ ከኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ የቀረበውን የሰላም ጥሪ ኤርትራ ልትቀበለው ይገባል፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደስልጣን ሲመጡ ከኤርትራ ጋር ያለውን ልዩነት ለመፍታት ለአቀረቡት የሰላም ጥሪ የኤርትራ ምላሽ እስከአሁን አዎንታዊ ሊሆን አልቻለም፡፡ የኤርትራ አቋም ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች የከፈሉትን አላስፈላጊ ዋጋ ከግምት ያላስገባና መፍትሄ የማያመላክት እንደሆነ ይገለጻል፡፡ 

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ልማትና አስተዳደር ኢንስቲትዩት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታቸው ዘሩ፤ ከዚህ ቀደም በሁለቱ አገሮች ድንበር ላይ ባካሄዱት ጥናት እንዳረጋገጡት ሁለቱ ሕዝቦች ካላቸው ጠንካራ ትስስር አንፃር የሕዝብ ለሕዝብ መስተጋብሩ ከፍተኛ ነው፡፡ ነገር ግን ባለፉት ሃያ ዓመታት በተፈጠረው ችግር በሕዝቦች ላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ አስከትሏል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ካላት ሰፊ ሕዝብ አንፃር የባህር በር ቢኖራት የሚያመጣላት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ኤርትራም ብትሆን አካባቢውን መዝጋቷ ከቀጣናው አገሮች ይልቅ ትስስሯን ከዓረብ አገሮች ጋር በማድረግ ከፍተኛ ጥቅም የምታገኝበትን ወደብ የተለያዩ አገሮች የጦር ስፍራ በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር መረሳ ፀሐዬ፤ ሁለቱ አገሮች ከተለያዩ በኋላ ኤርትራ በአገር ግንባታ እንዲሁም ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን በማረጋጋት በኩል ብዙ ተስፋ ቢጣልባቸውም ወደ ጦርነት መግባታቸው ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏል፡፡ ግጭቱ በሁለቱ አገሮች ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ቀንድ ቀጣናም ጭምር በስፋት የተንፀባረቀ ነው፡፡ ሁለቱ አገሮች ጦርነት ካቆሙ በኋላ ለዓመታት ያለ ሰላም ያለ ጦርነት በመዝለቃቸውም ኤርትራ ውስጥ ዜጎች የተለያዩ በደሎች እየደረሱባቸው ወደተለያዩ ዓለማት እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል፡፡
በተጨማሪም ይላሉ ተባባሪ ፕሮፌሰር፤ አለመግባባቱ ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ያሏትን አንፃራዊ ጥቅሞች እንድታጣ ምክንያት ሆኗል፡፡ በተለይም ከወደብ የምታገኘውን ጥቅም በጂቡቲ በኩል ማካካስ ብትችልም ከስፍራው ታሪካዊነትና ስትራቴጂካዊ ፋይዳ አንፃር ተጽዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ኤርትራም ብትሆን ለአገር ኢኮኖሚ ትልቅ ፋይዳ ያለውን ወደብ በመያዝ ብትነጠልም ወደቧን ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ልትመነዝረው አልቻለችም፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሑሩ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ፤ ያለፉት ሃያ ዓመታት በሁለቱ አገሮች መካከል ከኢኮኖሚና ፖለቲካ ጫና ባሻገር በሕብረተሰቡ መካከል መለያየትን አስከትሏል ይላሉ፡፡ ኤርትራ ነፃነቷን ስታገኝ የኢንዱስትሪ ማዕከል የመሆኗን ትልቅ አጋጣሚ ያጣችው በእነዚሁ ዓመታት ነው፡፡ ይሄም ለማገገም በሚያስቸግር መልኩ ከሌሎች ጎረቤት አገሮች ጋር ሳይቀር መተማመን አሳጥቷት ቆይታለች፡፡
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ ኢትዮጵያ በግጭቱ ያጣችው ወደብ ብቻ የሚመስላቸው ብዙ መሆናቸውን በመጥቀስ ነገር ግን ችግሩ ከወደብ በላይ አስተማማኝ ሰላም ባልሰፈነበት ድንበር አካባቢ ላሰፈረችው ጦር የምታፈሰው ሃብት እንደሚበልጥ ይናገራሉ፡፡
የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲው ረዳት ፕሮፌሰር ጌታቸው፤ አሁን በኢትዮጵያ ጥሩ የለውጥ ምልክቶች መታየት መጀመሩን እንደ መልካም አጋጣሚ ያነሱታል፡፡ እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጎረቤት አገሮች ሲያካሂዱ የቆዩት ዲፕሎማሲያዊ ይፋዊ ጉብኝት ምናልባትም ኤርትራን ሊያቀርባት ይችላል፡፡
ምንም እንኳን የኤርትራ መንግሥት ለድርድር ሽሽትን ቢመርጥም በአገሪቱ ሕዝቦች ዘንድ የሚስተዋለውን ሁለንተናዊ ቀውስ ከዓለም መሸሸግ አይችልም፡፡ ለዚህም ከኤርትራ ተፈናቅለው ወደ ጎረቤት አገሮች የሚሰደዱ ዜጎች ቁጥር መስካሪ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ኢትዮጵያ ከተቀ በለቻቸው 850ሺ ስደተኞች መካከል 160ሺ ወይም 19 በመቶ ኤርትራውያን ናቸው። ከዚህ ውስጥ 17ሺ 345 አካባቢው በአዲስ አበባ ይኖራሉ። እናም ሁለቱን አገሮች በአግባቡ የሚያደራድር አካል ከመጣ ችግሩን ለመፍታት ያስችላል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የተጀመረውን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ከነበረው በላይ ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ‹‹አጀንዳው ወደ ጠረጴዛ ይምጣ›› የሚለውን ሃሳብ ያጠናክራሉ፡፡ ሕዝባዊ ውይይቱ በተመሳሳይ በኤርትራም በኩል ከቀጠለ የሕዝቦች ፍላጎት ወደ መንግሥታት የማይቀየርበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡ ለዚህ ግን በቅድሚያ የኤርትራ ጉዳይ የኢትዮጵያውያን የውይይት ሃሳብ ይሁን፡፡ ይሄኛው አማራጭ ካልሰራ ኢትዮጵያ የኤርትራ መንግሥትን ለሚቃወሙ አካላት ድጋፍ በማድረግ ሥርዓቱን ለመቀየር የሚያስችል ጥረት ማድረግ ይጠይቃል ሲሉ መፍትሄ ይጠቁማሉ፡፡
ተባባሪ ፕሮፌሰር መረሳ፤ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ስትል በኤርትራ ውስጥ የስርዓት ለውጥ እስኪመጣ ድረስ የዲፕሎማሲ አካሄዶችን መከተል እንደሚጠበቅባት ያሳስባሉ፡፡ በዚህ ላይ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ አጋዥ ከመሆኑም በላይ ከጥቂት ዓመታት በፊት ሲነገርለት የነበረውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማሻሻያ በድጋሚ መመልከት ይጠበቃል፡፡
የዜጎች ውይይት ሲዳብር የውይይት ፍላጎቱ የኤርትራውያንም ፍላጎት እየሆነ በጋራ የመምከር ዕድል ይፈጥራል፡፡ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲው ኢትዮጵያ የተለያየ ግፊት እየፈጠረች የኤርትራ መንግሥት በግድ ወደ ድርድር እንዲመጣ ማድረግ መቻልም ሌላኛው አማራጭ ነው፡፡ ለዚህም በቅድሚያ ከሌሎች አገሮች ጋር ያላትን ዲፕሎማሲዊ አጋርነት ማስጠበቅ ይገባታል፡፡ እንዲሁም በአንፃራዊነት ከቀጣናው አገሮች የተሻለ መረጋጋት ስላላት ተመራጭነቷን በማጉላት ዕድሉን መጠቀም ይኖርባታል፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ከሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን ጋር ባደረጉት ውይይት የኤርትራ መንግሥት ለዓመታት ሲቀርብለት የቆየውን የሰላም ጥሪ ያልተቀበለው በግትርነት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያና ኤርትራ አንድ ሕዝብ ሁለት አገር ናቸው›› የሚሉት አቶ ኃይለማርያም፤ ወደ ስልጣን በመጡበት ወቅት የኤርትራ መንግሥት የሰላም ፍላጎት ካለው አስመራ ድረስ ተጉዘው እንደሚነጋገሩ ገልጸው ነበር፡፡ ከእርሳቸው በፊት የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በተመሳሳይ ለኤርትራ መንግሥት ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በተመሳሳይ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ይሄንኑ አቋም በድጋሚ አሰምተዋል፡፡ የኤርትራ መንግሥት ግን ለሁሉም ጥሪዎች ምክንያት እየፈጠረ አዎንታዊ ምላሽ አልሰጠም፡፡
ኤርትራ ለኢትዮጵያ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ አሻፈረኝ ማለቷ በሂደት የሚያስከፍላት ዋጋ ከፍተኛ ይሆናል፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ አሁን የመጣው አዲስ ፖለቲካዊ ለውጥ በኤርትራውያን ላይ መነቃቃት መፍጠሩ አይቀርም፡፡ መነቃቃቱ ደግሞ ኤርትራ ውስጥ ሕዝባዊ ጥያቄዎች እንዲበራከቱ ምክንያት ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል በአፍሪካ ቀንድ እየተስፋፋ ያለው የአረብ አገሮች የጦር ሰፈር ፍላጎት ተጠናክሮ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ጡዘቱ ሌላ መስመር ይይዛል፡፡ በዚህም ስጋቱ ቀጣናዊ መልክ በመያዝ ወትሮም ቢሆን የሰላም አየር በናፈቀው አካባቢ አዲስ መዘዝ ሊወልድ ይችላል፡፡  

ዜና ትንታኔ
ብሩክ በርሄ

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።