Items filtered by date: Friday, 11 May 2018

በሣይንስ ያልተደገፈ ልምምድ በየሜዳዎችና ተራራዎች ሲተገበሩ ማየት እየተለመደ ነው፡፡መስፈርቶችን ማዕከል ያላደረገ አካሄድ ስፖርቱን በባለፈው ክረም በሬ እንደሚባለው አይነት ለትችት ዳርጎታል፡፡ዓለምአቀፍ መስፈርቶችን ማዕከል ያደረገና በሣይንሳዊ መንገድ ልምምድ ቢደረግ የአትሌቲክስ ስፖርት አጓጊነቱ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ምንኛ የተሻለ በሆነ ነበር፡፡
እርግጥ ነው፣ አንድ አትሌት ችሎታው ከሕፃንነቱ ጀምሮ ለሯጭነት የሚያበቁ ሣይንሳዊ መመሪያዎችንና ትምህርቶችን በማግኘቱ ወይም ባለማግኘቱ ላይ ሊወሰን ይችላል፡፡ሆኖም ሯጮች ሣይንስን ያልተከተለ ልምምድ ማድረጋቸው ትክክል ወይም ስህተት፣ ተቀባይነት ያለው ወይም የሌለው እንደሆነ ማረጋገጥ የሚቻለው ከስር መሰረቱ የሣይንስ ስርጸት ሲኖር ነው፡፡
በተለያዩ ርቀቶች ላይ ሯጭ ሆኖ የቆየውና አሁን ታዳጊ ሯጮችን በሣይንሳዊ መንገድ በማሰልጠን ላይ የሚገኘው አሰልጣኝ ሙልዬ እያዩ እንደሚለው፤ የሩጫ ልምምድ በልምድና በዘመናዊ መንገድ ታግዞ ነው የሚከናወነው፡፡ሣይንስን የተከተለ የሩጫ ልምምድ ሲባል ዘመኑ የደረሰባቸውን ስልጣኔዎች አስተባብሮ መሄድ ሲሆን፤ የአትሌቱ የጤንነት ሁኔታ፣ ምቹ የአየር ንብረት መኖሩ፣ የልምምድ ሰዓት፣ የልምምድ ግብዓቶችንና ወዘተ…የሚያጠቃልል ሣይንሳዊ እሳቤ በአንድ ላይ ያያዘ ነው፡፡ እንደ ሩጫው የርቀት ዓይነት ማሟላት የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታ በሣይንሱ ውስጥ ይወሰናል፡፡ከዚህ አንፃር ውጤታማ ለመሆን ሣይንሱን ተከትሎ ልምምድ ማድረግ ይገባል፡፡ የስፖርት ሣይንስ እንደ ዓለም ዓቀፍ ያስቀመጠውን የልምምድ መስፈርት ተግባራዊ ማድረግ ባህል ተደርጎ ከቆየው ደመ ነፍሳዊ ልምምድ ለመውጣትም ያግዛል፡፡
እንደ አሰልጣኙ ምልከታ፤ በአሁን ወቅት ለማራቶን ሩጫ የ‹‹ኢንዱራንስ›› ልምምድ ስንት ኪሎሜትር በስንት ቀን ልዩነት እንደሚሰሩ ቢጠየቁ ብዙዎች አትሌቶች መልስ የላቸውም፡፡ ሳይንሱ የሚለውና አሁን እየተሠራ ያለው ልምምድ አይገናኝም፡፡
ሣይንሱን ተከትለው ለስምንት ዓመታት ልምምድ ያደረጉ አትሌቶች በዘመናዊ አሠራር ውስጥ ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ዘመናዊ የሚባለው ልምምድ ቅድመ ውድድር ላይ በቂ የዝግጅት ወቅት ማግኘትን ይጠይቃል፡፡ ይህም ከውድድር በፊት እስከ አራት ወራት ጊዜ ይወስዳል፡፡ በውስጡም ብዙ የልምምድ አይነቶችን ይይዛል፡፡በዕድሜና በጾታም ይወሰናል፡፡ በሣይንሳዊ መንገድ ከልጅነት ጀምሮ እስከ አዋቂነት እድሜ የሚሰጠው የልምምድ አይነት እንደየ እድሜው የሚሰጠው የልምምድ ደረጃ ይለያያል፡፡በእድሜው የሚመጥን የልምምድ አይነት እንዳይሰጥ ሳይንሱ ይከለክላል፡፡
አሰልጣኝ ሙልዬ እንዳለው፤ በዘመናዊ የአትሌቲክስ ስፖርት ሣይንሳዊ እሳቤ መሰረት፤ ልምምድ በቅድመ ውድድር፣ በውድድር ወቅትና ከውድድር በኋላ እንዲሠሩ ይመክራል፡፡ሣይንስን መሠረት አድርገው ለውድድር ዝግጅት የሚሠሩ ልምምዶች እንደ ሩጫው ርቀት የሚወሰን ሲሆን፣ ከሁለት እስከ አራት ወራት ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡በውድድር ወቅት የሚሠሩ ልምምዶች አትሌቱ ያለበትን ትክክለኛ አቋም ይወሰናል፡፡ ከውድድር በኋላ የሚሠሩ ልምምዶች ደግሞ አትሌቱ እንዳይጎዳና እንደ ማገገሚያ ተደርገው የሚሰጡ ናቸው፡፡
በአሰልጣኞች ድጋፍ በየምድቡ በሳምንታትና በወራት ምን ያክል መስራት እንደሚገባ ሳይንሳዊ የሆነ አስተምሮ መኖሩን እና እስከ ኦሎምፒክ ተሳትፎ የሚያደርስ ልምምድ ለማድረግ ከጀማሪነት ጊዜ ጀምሮ ሣይንሳዊ መስፈርቶችም መቀመጣ ቸውን አሰልጣኝ ሙልዬ ገልጿል፡፡ በአትሌቲክስ ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ ሣይንሳዊ አካሄድን መከተልና የብዙ ዓመት ልምምድ ማድረግ እንደሚገባም መክሯል፡፡
‹‹እነ እከሌ ሮጠዋልና እኔም ልሩጥ›› በሚልና ዘልማዳዊ ልምምድ ማድረግ አዋጭ አለመሆኑን የገለፀው አሰልጣኝ ሙሉዬ በሣይንስ ያልተደገፈ ልምምድ የሚያደርጉ ለሚሳተፉበት የውድድር ዓይነት ምን ያህል ኪሎ ሜትር መሮጥ እንዳለባቸው እውቀቱ እንደማይኖራቸው ተናግሯል፡፡እርሱ እንዳለው በሣይንስ የተደገፈ ልምምድ ባለመሆኑ ደክሟቸው ኃይል ሲያንሳቸው ይቆማሉ፡፡ልምምድ ሲያደርጉም በተደጋጋሚም በአንድ ቦታ ላይ ብቻ ይሠራሉ፡፡ አንድ አይነት ልምምድ ዳገት ላይ አሊያም ሜዳ ላይ ለሦስትና አራት ወራት እንደሚሠሩም ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡እንዴትና በምን ስልት የሚለውንም አያስተውሉም፡፡ ለአካል ጥንካሬ የሚሆኑ ልምምዶችንም አያደርጉም፡፡
እንደ አሠልጣኙ ማብራሪያ፤ ስማቸው የሚወሳው የአገራችን አትሌቶች አንዳንዶች ሣይንሱ በሚለው ሳይሆን እነርሱ በገባቸው መንገድ ልምምድ ሲያደርጉ ይታያል፡፡ በመሆኑም ውጤታቸው ዘላቂ አይደለም፡፡ በተወሰነ የውድድር መድረክ ብቻ ታይተው ይደክማሉ፡፡ ጤንነትን በመጠበቅ ላይ ተመስርተው በእቅድ ልምምድ የሚያደርጉ አትሌቶች ጥቂቶች ናቸው፡፡ በግላቸው ልምምድ በማድረግ ያለ መመሪያ የሚለማመዱም አሉ፡፡ አሰልጣኝ ካሠራቸው በኋላም ልምምዱ አንሶኛል በማለት ስፖርቱ ከሚፈልገው ዲሲፕሊን ውጭ ልምምድ የሚያደርጉ አሉ፡፡እንዲህ ያለው ልምምድ ስፖርቱን ከማቀጨጩ ባሻገር አትሌቱ ላይ ጉዳት ሊያስከትልበት የሚችል ጫና ይፈጥርበታል፡፡ በመሆኑም ባህላዊው ልምምድ ያለ እውቅና ስለሚደረግ ጉዳታቸው ያመዝናል ማለት ነው፡፡
ስህተቶች በማወቅም ባለማወቅም ይፈጠራሉ፡፡ ትልቁ ነገር ስህተቶቹን ለማረም ዝግጁ መሆን ነው፡፡ ልምምድ እንዴት መከናወን እንዳለበት ትምህርት ቢሰጥ ችግሩን መፍታት ይቻላል፡፡ትምህርት የሚሰጥ ተቋምም ሊኖር ይገባል፡፡አትሌቶች በየትኛው ሣይንሳዊ ፍልስፍና ውስጥ ማለፍ እንዳለባቸው ግንዛቤው እንዲኖራቸው ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ አሰልጣ ኞችንም በስፋት ማፍራት ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ የስፖርቱ ምሁራን ያስቀመጡትን መንገድ መከተሉ ይበጃል የአሰልጣኝ ሙሉዬ መልዕክት ነው፡፡
የሣይንሱ አስፈላጊነት እንደዛሬ ሳይነገር በህይወት የተለዩ ሥራቸው ግን ለትውልድ የተላለፈና የአገር ኩራትና ተምሳሌት የሆኑ አትሌቶች አይዘነጉም፡፡እነዚህ አትሌቶች በራሳቸው ተነሳሽነት ውጤታማ የሆኑ ናቸው፡፡ በወቅቱም አፍሪካንና መላውን የዓለም ሰው አስደምመዋል፡፡ ባህላዊ መንገድን የተከተለ ልምምድ ያድርጉ እንጂ የተለያየ የአየር ንብረት ያለባቸው ስፍራዎች ላይ ተንቀሳቅሰው ይሰሩ ነበር፡፡ የእነርሱ የልምምድ ስርዓት በወቅቱ እንጂ አሁን ላለንበት ነባራዊ ሁኔታ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡አብዛኛውን ጊዜ ይጠቀሙበት የነበረው የልምምድ ዘዴ በመካከለኛ ፍጥነት ላይ የተመሰረተና ድካም በተሰማቸው ወቅት ልምምዱን ያቆማሉ፡፡ምንም እንኳን የተወሰኑት ውጤታማ መሆን ቢችሉም ልምምዱ ግን ሣይንሳዊ አልነበረም፡፡
አሰልጣኝ ሙሉዬ እንዳለው አሁን እየተሠራ ባለው ልምምድ ብዙኃኑ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በልጅነታቸው በባህላዊ ልምድን ውስጥ ያለፉ ናቸው፡፡ በመሆኑም ጉልበታቸውን በጊዜ ይጨርሳሉ፡፡በዚህ ከቀጠለና መፍትሄ ካላገኘ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡በአገር አቀፍ ደረጃ ምክክር በማድረግ ዘርፉ ሳይንሳዊ በሆነ አሠራር መከናወን አለበት፡፡የአትሌቲክስ ስፖርት ዕድገትም የራሱ መዋቅር ያስፈልገዋል፡፡ ከመካከለኛ ርቀት ወደ ረጅም ርቀት ከዚያም ወደ ማራቶን ደረጃውን የጠበቀ እድገት መፈጠር ይኖርበታል፡፡ አንድ አትሌት ማራቶን መሮጥ ያለበት በስንት ዕድሜው እንደሆነ አትሌቶችም አሰልጣኞችም ሊያውቁት ይገባል፡፡ በ20 ዓመታቸው ማራቶን የሚሮጡ አትሌቶች አንድ ጊዜ ከሮጡ በኋላ ሌላ ውድድር ለመካፈልና ውጤታማ ለመሆን ይቸግራቸዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ አንዳንድ አትሌቶችን ለዶፒንግ ተጠቃሚነት ሊገፋፋቸው ይችላል፡፡
አሠልጣኙ እንደሚለው፤ ዘመናዊ ስፖርት ከልምድ የተወሰደ ቢሆንም፤ ነባራዊው የሆነውን የዓለም ሁኔታ አገናዝቦ ለመስራት ግን ሣይንሱን በጉልህ ማስቀደም ይገባል፡፡ በዚህ ሂደት ልምድን ወደ ዘመናዊነት በመቀየር ሩስያና የሩቅ ምስራቅ አገሮች የተሻሉ ናቸው፡፡ሀገራቱ በባህላዊና በዘመናዊ መንገድ ልምምድ ውስጥ ያለፉትን አትሌቶችን በማነፃጸርና ሁለቱንም በማስታረቅ ሣይንሳዊውን መንገድ በመከተል በተወሰነ ውጤት ማግኘት አስችሏቸዋል፡፡
አበረታች ቅመም የማይወስዱ፤ የጅምናዚ ዬም ልምድ ያላቸው፤የተመጣጠነ አመጋገብ ያላቸው ፣ ፣የስፖርት ሳይንሱን ለመተግበር ዝግጁ የሆኑ፣መቼ እረፍት ማድረግ እንዳለባቸው የሚያውቁ፣ በሥነምግባር የታነጹ፣ከሌሎች ተሞክሮ ለመወሰድ ፈቃደኛ የሆኑ አትሌቶችን በስፋትና በጥራት ማፍራት እንደሚገባ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
ሣይንሳዊ መሰረት የሌለውን ልምምድ የሚያደርጉ የአትሌቶችን በቅርበት መቆጣጠር በዋናነት የአሰልጣኞች የሥራ ኃላፊነት እና ድርሻ መሆን እንዳለበትም ገልጿል፡፡ የአሰልጣኝ ሥራው የውድድር መርሐ ግብር ሰጥቶ ብቻ መቆጣጠር መሆን እንደሌለበትም ተናግሯል፡፡
በሣይንሳዊ ስልጠና ሂደት ውስጥ አንድ አሰልጣኝ የሚያሰለጥናቸውን አትሌቶች የፍቅር ወይም የትዳር ግንኙነት፤ ከቤተሰቡ ጋር ያለውን ሁኔታ ማጤንና በልምምድ ሰዓት ከጭንቀት እና ከማናቸውም ውጥረት ውጭ ለመስራት ያለውን ዝግጁነት መረዳት እንዲሁም የአትሌቶችን የዕለት ተግባራት፤ እንቅስቃሴ፤ የልምምድ መርሃግብርና አፈፃፀም በዝርዝር መመዝገብ እንደሚጠበቅበትም አስረድቷል፡፡ ሣይንሳዊ የስልጠና ስርዓት ተከትሎ ወቅታዊ ብቃትን በመገምገም መሥራት አትሌቱን ብቁ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ባለ ድርሻ አካላት ሳይንሱ እንዲተገበር በጥናት እና ምርምር በመደገፍ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊያደርጉ እንደሚገባም ተናግሯል፡፡
አሰልጣኞች እና በየአካዳሚው የሚሰሩ ባለሙያዎች ደረጃውን የጠበቀ የስልጠና ፖሊሲን እና ዘመናዊ አካሄድን መፈጠር፣የምልመላ፤ የውድድር አይነት አመዳደብ ፤ የስልጠና ደረጃዎች እና ሂደቶች ላይም አገር አቀፍ መመሪያ ማዘጋጀት እና ሥራዎችም በየጊዜ የሚገመግሙበትን አሠራር ማመቻቸት እንደሚገባ አሰልጣኝ ሙሉዬ ገልጿል፡፡

 

13ሺ ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉበት ማጠቃለያ ሩጫ እሁድ ይካሄዳል

 

ታላቁ ሩጫ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር የባንኩን 75ኛ ዓመት ምስረታ በዓል አከባበር አስመልክቶ ውድድሩን ሲያካሂድ መቆየቱንና እሁድ እንደሚጠናቀቅ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የውድድርና ኦፕሬሽን ኃላፊ አስታወቁ፡፡

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የውድድርና ኦፕሬሽን ኃላፊ አቶ ዳግም ተሾመ፤ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤የባንኩን 75ኛ ዓመት ምስረታ በዓል አከባበር አስመልክቶ በበጀት ዓመቱ በመቀሌ፣ በባህር ዳርና በሀዋሳ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን፤ ሰባት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍንና 13ሺ ሰዎች የሚሳተፉበት የማጠቃለያ የሩጫ ውድድር የፊታችን እሁድ በአዲስ አበባ ከተማ ያካሄዳል፡፡
ውድድሩ የክብረበዓል መሆኑ ለየት ያደርገዋል ያሉት አቶ ዳግም በባንኩ ያገለግሉ የነበሩ የ75 ዓመት አዛውንቶች የአምስት መቶ ሜትር ውድድር እንደሚያካሂዱና ልዩ ሽልማት እንደሚያገኙ ገልፀዋል፡፡
በሩጫው ወቅት የሚተላለፉ መልዕክቶች አስተማሪ ከመሆናቸው በተጨማሪ የውድድር መድረክ ላላገኙ ዕድል የፈጠረና በየክልሉ የሚገኙ አትሌቶችን በተወሰነ ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ባንኩን ከመዘከር ባሻገርም ስፖርታዊ ፋይዳው የላቀ መሆኑንና እንዲህ አይነት ውድድሮችን ማካሄድ ህብረተሰቡ ጤናውን እንዲጠብቅና በስፖርት ላይ ያለውን የተሳትፎ ልምድ ከፍ ለማድረግ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡ ባንኩ የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓሉን ከሚያከብርባቸው መርኀ ግብሮች መካከል በስፖርት የበለጸገ ማህበረሰብን ማፍራት አንዱ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሲቋቋም ዋና ዓላማው ህዝባዊ ውድድሮችን በአገሪቱ ማካሄድ ነው።
በክልሎች በተደረገው ውድድር ላይ ከአንደኛ እስከ አስረኛ ደረጃ ለወጡ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት መበርከቱንም አስታውቀዋል፡፡ እሁድ የሚካሄደው ሩጫ የአሸናፊዎች አሸናፊ መሆኑና አዲስ አትሌቶች እንደሚታዩበትም ገልጸዋል፡፡
በማጠቃለያ ውድድሩ ላይ በሦስቱ ክልል በተደረጉ ተሳትፎዎች ላይ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ የወጡ ስፖርተኞች፣ የባንኩ የረጅም ጊዜ ደንበኞች የሆኑ፣ 75 ዓመት የሞላቸው አዛውንቶች፣ የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ ዳይሬክተሮች፣ ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጆች፣ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ደንበኞች፣ በኢትዮጵያ የቅድሚያ ለሴቶች ሩጫ ላይ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ የወጡ እንዲሁም በ2010 የኦሮሚያ ሻምፒዮና በ10ሺ ሜትር ውድድር ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ የወጡ አትሌቶች እንደሚሳተፉ አቶ ዳግም ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ዳግም ገለጻ፤ የውድድሩ መነሻና መድረሻ መስቀል አደባባይ ሲሆን፤ 7 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል፡፡ በዚህ ርቀት አሸናፊ ለሆኑ የ75ሺ ብር ሽልማት ይሰጣል፡፡ ይህም ታላቁ ሩጫ ከሚያዘጋጀው ከዋናው ፕሮግራም ቀጥሎ በተሳታፊ ቁጥርም ሆነ በገንዘብ ሽልማት ሁለተኛው ነው፡፡
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ታላቁ ሩጫ ግንኙነት የፈጠሩት በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2009 ጀምረው ሲሆን፤ በተባባሪና ዋና ስፖንሰርነት ከአሥር ዓመት በላይ የዘለቀ አጋርነት መስርተዋል፡፡

አዲሱ ገረመው

 

ብሄራዊ ቡድኑ የገንዘብ ድጋፍ በማጣቱ ያለ በቂ ልምምድ ወደ ዑጋንዳ ሊያቀና ነው

 

በዓለም አቀፍ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት በዑጋንዳ ለሚካሄደው የ2018 የዞን አምስት ውድድር የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ብሄራዊ ቡድን ያለ በቂ ዝግጅት ወደ ሥፍራው ሊያመራ መሆኑ ተገለፀ፡፡
የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ፍትህ ወልደሰንበት በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት እና ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን በዑጋንዳ ለሚካሄደው ዞን አምስት ውድድር ለመካፈል ከዓለም አቀፍ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን ግብዣ ቀርቦለታል፡፡ ይሁንና አሰልጣኞችና የቡድን መሪዎችን ጨምሮ 34 ልዑካን የተካተቱበት ቡድኑ በፋይናንስ እጥረት ምክንያት በቂ ዝግጅት ሳያደርግ ወደ ሥፍራው ለማቅናት እንደሚገደድ ጠቁመዋል፡፡
አቶ ፍትህ እንዳሉት፤ ተጨዋቾች ወደ ሆቴል ገብተው ዝግጅትና ልምምድ ለማድረግ ወጪውን እንዲሸፍኑ ከአንድ ሚሊዮን ብር ያነሰ ድጋፍ ቢጠየቅም በጎ ምላሽ ማግኘት አልተቻለም ፡፡ በዑጋንዳ ለሚኖረው ቆይታ የአውሮፕላን ትኬትን ጨምሮ ለዚህ ውድድር አጠቃላይ ወጪ የሚሸፈነው ከዓለም አቀፍ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን ነው፡፡ ነገር ግን ቡድኑ ለዝግጅት በሚያደርጋቸው መርሐ ግብሮች ሙሉ ወጪ የሚሸፈነው በአገር ውስጥ ወጪ ነው፡፡ ይሁንና ፌዴሬሽኑ በራሱ በጀት ይህን ለማከናወን አቅም የሌለው በመሆኑ ሌሎች አካላትን ለመጠየቅ ተገዷል፡፡ በዚህ መሰረት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር እና ኦሎምፒክ ኮሚቴ ድጋፍ እንዲያደርግ ፌዴሬሽኑ ቢጠይቅም አንዳችም አዎንታዊ ምላሽ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ምንም እንኳን ፌዴሬሽኑ በርካታ ተግባራትን ለማከናወን በሚደርገው ጥረት እክል ቢገጥመውም፤ ችግሮቹ በማራግብ ሌሎችን የመውቀስ ዓላማ እንደሌለው በመግለፅ፤ በቀጣይ ሊጤን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ እንደገለፁት፤ ስፖርተ ኞቹ ያለ ምንም ዝግጅት ወደ ዑጋንዳ ማምራት እንደሌለባቸው ፌዴሬሽኑ በማመኑም ለጥቂት ቀናት ቢሆንም፤ አማራጮችን በመጠቀም ልምምድ እንዲያደርጉ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በመሆኑም ከሚቀጥለው በጀት ዓመት ሊከፈል የሚችል ክፍያ ከግምት ውስጥ በማስገባት በብድር መልክ ከሆቴሎች ጋር በመግባባት ስፖርተኞቹ ከግንቦት 1እስከ4 ቀን 2010 ዓ.ም ሆቴል እንዲገቡ በሥራ አስፈፃሚው ከስምምነት ተደርሷል፡፡
አቶ ፍትህ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያን ወክለው በዑጋንዳ ለሚሳተፉ ከ18 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ለልልምድ ወቅት 350ሺ ብር የተጠየቀ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ፤ ከ20 ዓመት በታች የብሄራዊ ቡድን ስልጠና ወቅት 350ሺ ብር በድምሩ 700ሺ ብር ተጠይቆ ነበር፡፡ ይሁንና ከአንድም አካል በቂ ምላሽ ባለመኖሩና የበጀት እጥረት አጋጥሞናል በሚል ሰበብ ብሄራዊ ቡድኑ በቂ ልምምድ ለማድረግ አልቻለም፡፡ ይሁንና ፌዴሬሽ በደረሰበት ውሳኔ መሰረት ለበቂ ልምምድ የሚመጥን ባይሆንም በብድር መልክ ለጥቂት ቀናት በሆቴል ለሚደርገው ቆይታ 137ሺ ብር እንደሚያስፈልገው ጠቁመዋል፡፡
ወደ ኡጋንዳ የሚያቀኑት ክለቦች ሳይሆኑ የአገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልቡ ብሄራዊ ቡድኖች በመሆናቸው፤ ድጋፍ ሊደረግ ይገባ እንደነበር አስገንዝበዋል፡፡ ለእጅ ኳሱ እየተደረገ ያለው ድጋፍ አነስተኛ በመሆኑ በቀጣይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባልም ብለዋል፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት በዞን አምስት ውድድር ኢትዮጵያ በወንዶችና ሴቶች ስትሳተፍ የቆየችና ዋንጫ ማንሳት የቻለች አገር መሆኗን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፤ በዚህ ዓመት ዓለም አቀፍ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን አሠራሩን በመቀየሩ ወንዶች ብቻ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል፡፡
ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ እንደሚያመ ለክተው፤ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ዓመታዊ በጀት 380ሺ የማይበልጥ ሲሆን፤ ይህም ፌዴሬሽኑ የሚፈለገውን ተግባር እንዳያከናውን ጫና ፈጥሮ በታል፡፡ በዞን አምስት ውድድሩ 11 አገራት የሚሳተፉ ይሆናል፡፡

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

Published in ስፖርት

‹‹ሆድ ከሀገር ይሰፋል›› ቢልም ብሂሉ ከትንሹ የእናትነት አለም ስጋ ተነስተን ነፍስ ዘርተን ህይወትን ለመኖር ከውቅያኖስ እልፍ ጊዜ ወደሚሰፋው አለም መጣን፡፡ ወደዚህ አለም መጥተን ስንደባለቅ የመኖር ፍቅራችን ይጨምራል፡፡ በውስጧ እትብታችንን ያዘለችው መሬት እዚሁ በዚሁ የመኖራችንን ነገር አሻሽላ ትጠብቀናለች፡፡ ከምድር አፈር ተበጅተን ወደ ምድር በመጣን ጊዜ በላባችን ጥረንና ግረን እንድንበላ ተፈርዶብናል፡፡ (በላባችን የምትለዋ ይሰመርባት) ከዚያም በምላሳችን ጥረን ግረን የሚለው ስለሚቸግረኝ ለፍልፈን እንድልበላ የታዘዝንም መኖራችንን ለማሳየት ነው መሰለኝ ይኸው በግብር ተወራራሽነት ምላስ ከጉልበት ልቃ ከምራቅ ይልቅ ላብ አመንጭታ የደላላ ሁነኛ መሳሪያ ሆና እንድትኖር ተደርጋለች፡፡

ጓደኛዬ እለተ እሁድን እንደማይወደው አሳምሬ አውቃለሁ፡፡ በእሁድ ምድር ለመዝናናት ብለን ከመንደራችን የራቅንበትን ጊዜ ብዙም ትዝ አይለኝም፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሙታኖችን መታሰቢያ ሀውልት ለመመረቅ በአርባና በሰማኒያ ሰበብ ከቤት ብንወጣም ብዙ ጊዜ ጠዋት ስለሚሆን ትዝብቴ ያን ያህል አይደለም፡፡ በጣት የሚቆጠሩ ቁርባኖች ግን አስገርመውኛል፡፡ ሁለት ሶስት ሰንጋ ተጥሎ ጮማ እየቆረጥን ጠጅና ጠላ የጠጣንበት የሙታን መታሰቢያ ልበለው የሙታን ሰርግ ማለፊያ ነበር፡፡
ታዲያ እሁድን ምን አስመለከተህ እንዲያው ምን ትዝ አለህ ትሉኝ ይሆናል፡፡ ይህ ቀን ለመዝናናት ቀርቶ ለመብላት እንኳን ፋታ አልሰጠኝም፡፡ እንደልማዴ ከምኖርበት ባለ ሁለት መኝታ ማለቴ ባለ ሁለት እርምጃ ቤት ተላቅቄ ሌላ ሰፋ ያለ ቤት ፍለጋ ታዋቂ ደላላ ነው ተብዬ የተጠቆምኩበት ቦታ አመራሁ፡፡ በዚሁ በእለተ እሁድ ማለት ነው፡፡
ከአይነ ገብ ባለብዙ ቀለም ቲሸርት ላይ ከተገዛ አንድ የምርጫ ዘመን ያሳለፈ የሚመስል ጥቁር ሌዘር ጃኬቱን ለብሷል፡፡ ወንበር ስር ስለተደበቀ ከወገብ በታች ያለውን አለባበሱን ከመቀመጫው እስከሚነሳ ድረስ በውል አላስተዋልኩትም፡፡ የለበሰው ሱሪም ቀለሙ ከጥቁርነት ወደ ቡኒነት ተለውጦአል፡፡ (ከተነሳ በኋላ ያየሁት) ጥቁር ሹል ጫማው በ ‹‹ስፔሻሊስት›› ሊስትሮ የተወለወለ ይመስላል፡፡ ያለ ጸሀይ በደብዛዛው ቤት ውስጥም ያበራል፡፡ ወደ ቀይ የሚያደላ መለዮም አድርጓል፡፡ ጥቁር መነጽሩም ከአፍንጫው በታች ወርዶ አፉን ሊነካው ምንም አልቀረውም፡፡ (ትንሽ አጋንኛለሁ)
ለሰላምታ እጄን ከመዘርጋቴ በፊት መነጽሩን ከአፍንጫው ላይ ማለቴ ከአፉ ላይ አንስቶ ምላሱን ዘረጋው፡፡ ‹‹…ኑሮህን የምታቀልልህ፣ በወጣህ በገባህ ቁጥር እንክብካቤ እንጂ ጭቅጭቅ ፈጽሞ የማታውቅ፣ ካንቺ ውጭ ሚስት አማረኝ ብትላት እንኳን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ሌላ እንድትሄድ የምትፈቅድልህ፣ ስለ ፍቅሯ ከሰማይ ቤት የጥራት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የተሰጣት… ታጥባ የተቀሸረች ደረጃ አንድ ምርጥ የማይገልጻት ሚስት አሁኑኑ አገናኝሃለሁ…›› አለኝ፡፡ ለምን እንደመጣሁ እንኳን ሳይጠይቀኝ፡፡ ፍጥነቱ ደግሞ የቤተሰብ ጨዋታን ከሚያስተዋውቀው አርቲስት ነጻነት ሁለት እጥፍ ነው፡፡
በእርግጥ ሚስት በደላላ መገኘቷን አግብተው ከተፋቱ ሰዎች ሰምቻለሁ፡፡ ምንም እንኳን ነገሩ አዲስ ባይሆንም የኔን አመጣጥ ሳይጠይቅ መቀባጠሩ ግራ ገባኝ፡፡ አውቃለሁ ደላላ ብዙ ይዘላብዳል፤ እንደዚህ ግን ገጥሞኝ አያውቅም፡፡ በሬ ወለደ አይነት ወሬው ‹‹መርዝ ማስቲሽ›› ብዬ እንድጠራው አድርጎኛል፡፡ ምኑን ከምኑ እንደሚያገናኝ አይታወቅም፡፡
ቤት ፍለጋ እንደመጣሁ ነገርኩትና ተረጋግቶ እንዲያወራኝ ተማጸንኩት፡፡ ፋታ ሳይሰጥ ቀጠለና አርሰናል ለመጨረሻ ጊዜ ዋንጫ ሲበላ በወቅቱ ዘመናዊ የነበረችውን ኖኪያ ስልኩን ከደረት ኪሱ አውጥቶ ደወለ፡፡ ‹‹ እንደምን አሉ ወይዘሮ እከሊት… አቶ እከሌ እንዴት ያሉ ደግ መሰሎት (አንድ ቀን ብቻ አይቶኝ) እንኳን እርስዎ ሰማይ ቤት ያሉ ሙታን ያውቋቸዋል፡፡ (ሲኦል ያሉትን አይደለም) አገርን በገንዘብ ያቀና ጀግና ሰው ነው ወዘተ… እያለ ምን አይነት ቤት እንደምፈልግ እንኳን ሳይጠይቀኝ ምላሱን በኪሎ ሜትሮች ዘርግቶ ሴትዮዋን አሳምኖ ሲጨርስ ወደ እኔ ዞር አለ፡፡
አሁን እኔም ንዴቴ ባስ ሲልብኝ ቆይ ሳያጣሩ ወሬ መንዛት ወንጀል መሆኑን ታውቃለህ አልኩት ‹‹ከእያንዳንዱ ሀብት በስተጀርባ ወንጀል አለ ሲሉ አልሰማህም›› አለኝ ተግባሩን ቀባብቶ ለማለፍ፡፡ ታዲያ ለምን ይሄንን ስራ ትተህ ሌላ ስራ አትሰራም አልኩት ድንጋይ መፍለጥንም አስቤ፡፡ ‹‹ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ነገር ግን እኔ መኖር እንጂ መሞት አልፈልግም፡፡ ለመሞት የተዘጋጀ ሰው የጉልበት ስራ ይስራ፡፡ እያለ ሹፈቱን ቀጠለ፡፡ እንዲህ በአፈ ቀላጤነት እየሸወዱ ከመኖር ይሻላል፡፡ ለምን ታክሲ እንኳን እየነዳህ አትተዳደርም አልኩት ከላዳ ታክሲ የሚገኘውን ጥቅም አስቤ፡፡ ንግግሬን ሳያስጨርስ ‹‹ባክህ ከተማ ውስጥ ተሯሩጬ ‹‹ላዳ ሰርቶ ለባዳ›› መባል አልፈልግም፡፡ ላዳ ለባለቤቱ እዳ ነው እኮ፡፡ ሲለኝ ይህንን ሀሳብህን ሰው የማይደርስበት ቦታ ላይ ጣለው አልኩትና ወዛደርነትንስ ለምን አትሞክርም አልኩት፡፡ (ነገረ ስራው የመጣሁበትን ዓላማ አስረስቶኛል)
ለዚህ ጥያቄ በጎ ምላሽ እንደማይሰጠኝ አውቃለሁ፡፡ ምክንያቱም ብዙዎቻችን ወዛደር አለመሆን ብቻ ሳይሆን፤ ስሙን ለመጥራት እንኳን እናፍራለን፡፡ እንደውም አንድ መምህር በአንድ ወቅት ተምረህ ምን መሆን ትፈልጋለህ? ተብሎ ‹‹ወዛደር›› ያለ ተማሪም አላጋጠመኝም፡፡ ብሏል፡፡ በእርግጥ ተማሪው ‹‹ወዛደር››ብሎ የወደፊት ምኞቱን ቢናገር እንኳን መምህሩ እና ወላጆቹ ወዛደር ይሆን ዘንድ አይፈቅዱለትም፡፡ ምክንያቱም ወዛደርነት የሰነፍ፣ የዱርዬ፣ የአውታታ ወይም ተስፋው የተሟጠጠ ሰው ሥራ ተደርጎ ተቆጥሯልና፡፡ በዚህ ምክንያት የወዛደር ልጅ መባል ሀፍረት እንጂ ደስታ የማይሰጥ ሆነ፡፡
ደላላውም ጥያቄዬን ወዲያ አሽቀንጥሮት ወደ ምላሱ ተመለሰ፡፡ አስቀድሞ ወረፋ ስለያዘው ቤት ተከራይ በስልክ ያግባባ ጀመር፡፡ ‹‹… ብቻ ጌታዬ! ጋሽ ዘሪሁን ለኔ የረዥም ዘመን ደንበኛ ብቻ ሳይሆን ጀግና ሽማግሌ ናቸው፡፡ ጥረውና ግረው የሚያድሩ ፤ ለትውልድ የሚቆይ ቅርስ ያቆሙ የልማት ታጋይ ብንላቸው ይቀለኛል፡፡ ከብርታታቸው የተነሳ የእርሳቸው ስም የእድርና የሰፈር ስም ለመሆን የበቃ ነው፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ የታክሲ ረዳቶች ሳይቀሩ በግድ ስማቸውን በቀን ሺ ጊዜ ይጠሯቸዋል፡፡…›› እያለ ያወራል፡፡ እኔንም ረስቶኛል፡፡ ስልኩን አውርቶ ሲጨርስ ጉዳዬን ለማንሳት አፌን ከፈት ከማድረጌ ‹‹በል በል አየር አትያዝ›› እስካሁን ያወራሁበትን ከከፈልከኝ ብቻ መደራደር እንችላለን አለኝ፡፡ በእሁድ ቀን ክፉ እንዳይወጣኝ ብዬ በሆዴ ብቻ ረግሜው ከፊቱ ዞር አልኩኝ፡፡
ደላላ ተብለው ተደራጅተዋል ከምላስ በስተቀር አስር ኪሎ ቋጠሮ መሸከም የሚችል ጉልበት እንኳን አልተወላቸውም፡፡ ዘመነ ሉላዊነት የአፋሞች ጊዜ ሆኗል፡፡ በዚህ ዘመን ላብ (ጉልበት)ለሰው ልጅ ኑሮ ምንም ፋይዳ እንደሌለው ያየሁት በእነርሱ ነው፡፡ በአፈቀላጤነት ውስጥ ያሉ ብዙዎች የሚበሉት እንጀራ በላባቸው የጋገሩት ሳይሆን በወሬ ጥፍጥናቸው ያበሰሉትን ነው፡፡ በየሰፈሩ እየዞሩ ወሬውን እንደውድ ማዕድን ለአከራይ ተከራይ፣ ለተጋቢዎች፤ ለሻጭና ገዢዎች… እየመነዘሩ ኑሮአቸውን ይመራሉ፡፡
አጥንትም ጅማትም ያልተፈጠረባት ምላሳቸው ከመገጣጠሚያ የቁርጥማት በሽታ (ሪህ) ነፃ ስለሆነች ሌላው አካላቸው እየሰለለ እንደልብ መራመድ እንኳን ሲከዳቸው እሷ ግን ከጉልበት ላይ ጉልበት ከኃይልም ላይ ኃይል ትጨምርላቸዋለች፡፡ እናም በየቀኑ እግራቸው ከዕለት ወደ ዕለት እያጠረ ምላሳቸው ደግሞ እየረዘመች ትመጣለች፡፡ ‹‹ምላስ ያለው ያግባኝ ›› አለች የተባለው ትንቢት አሁን ተፈጸመ ማለት ይህ ነው፡፡

አዲሱ ገረመው

 

Published in መዝናኛ

መኪና፣ ባቡር፣ አውሮፕላን፣ የመሳሰሉ የየብስና የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቶች፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫ፣ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች፣ የኬሚካል ምርቶችና ሌሎችም ትላልቅ የኢንደስትሪ ውጤቶች ከነዳጅ እና ማዕድን ቀጥሎ ከፍተኛ ዶላር የሚያስገኙ የሀብት ምንጮች ናቸው፡፡ እነዚህ የሀብት ምንጮች የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሲሆኑ፣የሰው ልጅ በትምህርት ያገኘውን ክህሎትና የተፈጥሮ ተሰጥኦውን ተጠቅሞ የሚያከናውናቸው መሆኑ ደግሞ የቴክኖሎጂን ጥቅም ያጎላዋል፡፡
ቴክኖሎጂ ለአንድ ሀገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ እንዲሰራ እያከናወነ ስላለው ተግባር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቋሚ ጉዳዮች ኮሚቴ ገለፃ አድርጓል፡፡
በወቅቱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢኒንጂነር ጌታሁን መኩሪያ እንደተናገሩት፤ በተፈጥሮ ነዳጅ ሀብታም የሆኑ ሀገራትን ሳይጨምር በእያንዳንዱ የምርት አገልግሎታቸው ላይ በቴክኖሎጂ የታገዘ እሴት በመጨመር የወጭ ንግዳቸውን ያሳደጉ ሀገራት በርካቶች ናቸው፡፡ ሀገራቱ ኢኮኖሚያቸው ሙሉ ለሙሉ የሚመነጨው ከኢንደስትሪ ውጤቶች ሲሆን፣ከኢንደስትሪው በሚያገኙት ገቢ የግብርና ግብአቶችን ከውጭ በማስገባት ህዝባቸውን ይመግባሉ፡፡ ይህን ወደ ሀገሪቱ ማምጣት ያስፈልጋል፡፡
«ቴክኖሎጂ ሩቅና ከባድ ተደርጎ መታየት የለበትም» ያሉት ሚኒስትሩ ቴክኖሎጂን መጠቀም እድገት ሲኖር ብቻ እንዳልሆነ ከፍ ያለ ተሞክሮ ያላትን አየርላንድን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ ሀገሪቷ የፅህፈት ሥራን በቀላሉ ለማከናወንም ሆነ በዓለም ላይ የተለያዩ መረጃዎችን ለማግኘት የሚያስችለውን ኮምፒውተር መስራት የጀመረችው ገና ኢንደስትሪውን ስትቀላቀል እንደበርም ገልፀዋል፡፡
ቴክኖሎጂን በመጠቀም በጊዜ፣በጉልበትና በገንዘብ የሚወጣውን ወጭ መቀነስ እንዲሁም ከፍተኛ ሀብት ማፍራት እንደሚቻል የጠቆሙት ሚኒስትሩ ለአብነት ካነሷቸው መካከል የህንፃ ግንባታ ሥራ ይገኝበታል፡፡በብዙ ሀገሮች ለመኖሪያና ለተለያዩ አገልግሎቶች ለሚውሉ ህንፃዎች ግንባታ የሚያገለግሉ ቁሶች በፋብሪካ ውስጥ ነው የሚያልቁት፡፡ አሰራሩም የግንባታ ብክነትንና ወጭን ከመቀነሱ በተጨማሪ በግንባታ ዕቃ መንገድ መዝጋትን ያስቀራል፡፡ አካባቢንም አይበክልም፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ ቴክኖሎጂ የማይዳስሰው ዘርፍ ባለመኖሩ በቴክኖሎጂ የታገዘ ሁሉ ሀብት ያመነጫል፡፡ ከዚህ አንፃር መረጃም «ኢንፎርሜሽን» የሀብት ምንጭ ነው፡፡ኢኮኖሚያቸውን በግብርና ላይ ለመሠረቱ ሀገሮች መረጃ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ የዝናቡ መጠን፣ጎርፍና ወረርሽኝ መኖሩን፣አንበጣ መከሰቱን፣ በአጠቃላይ ለእርሻ ሥራው ተስማሚ የአየር ፀባይ መኖርና አለመኖሩ በቴክኖሎጂ የታገዘ መረጃ ተደራሽ ሲሆን ውጤታማ መሆን ይቻላል፡፡ ለከተማውም ቢሆን ዝናብ የት አካባቢ እንደሚዘንብ በመጠቆም ጤናማ እንቅስቃሴ መፍጠር ይቻላል፡፡
ተሞክሮዎችን በኢትዮጵያ ለማየት እሩቅ እንደማይሆንና በሚኒስቴሩ የተተገበሩና በመተግበር ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን በተመለከተም ሚኒስትሩ በቅደም ተከተል አስረድተዋል፡፡ ከተተገበሩት መካከልም የመረጃ ሥርአት አንዱ ነው፡፡ በሚኒስቴሩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል ውስጥ የአየር ንብረት መለኪያ ስድስት ክፍሎች ተደራጅተዋል፡፡ እነዚህ ክፍሎች «እሴት የተጨመረበት ፋብሪካ» ማለት እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡
በቅርቡ ለአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ያስረከበው ቴክኖሎጂ ወይንም የሳይንስ ካፌ ይጠቀሳል፡፡ ስለ ካፌው እንዳስረዱት በካፌው ውስጥ አፈር ሳያስፈልግ አትክልትና ፍራፍሬ ማምረት ይቻላል፡፡እንደመፅሐፍ መደርደሪያ በመጠቀም በቤት ውስጥ የተለያዩ ምርቶችን ለማምረት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው፡፡ የቴክኖሎጂ ካፌው ወጣቶችን ማዕከል አድርጎ የተሰራ ሲሆን፣ወጣቶቹ ቴክኖሎጂውን እየተማሩ የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ዓላማ ተደርጎ የተቋቋመ ነው፡፡ ወጣቶቹ ቴክኖሎጂ ይማራሉ፤ በተማሩት ገቢ ይፈጥራሉ፡፡ በዚህ መንገድ በሚስፋፋው የከተማ ግብርና ተጠቃሚው በቀላሉ ንፁህ የሆነና ያልተበከለ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ያገኛል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የተሰሩት የቴክኖሎጂ ካፌዎች አምስት ሲሆኑ፣በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይና በደቡብ በተመሳሳይ አምስት ተጨማሪዎች እየተሰሩ ናቸው፡፡ በዚህ መልኩ በሌሎችም ተሞክሮውን በማስፋፋት ወጣቱን ተጠቃሚ የማድረጉ ሥራ ይጠናከራል፡፡
በሌላ በኩልም ሚኒስቴሩ በትንሽ ግኝት ብዙ የዓሣ ሀብት ሊያስገኝ የሚችል ሥራ ለመስራትም ቅድመ ሁኔታዎችን አመቻችቷል፡፡ ሚኒስትሩ እንዳሉት በኃላ ቀር ዓሣ የማስገር ሥራ የትም አይደረስም፡፡ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ ተፈላጊ የዓሣ ሀብት ቢኖራትም በቴክኖሎጂ መጠቀም ባለመቻሏ፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በምግብ ሸቀጦች መሸጫና ባለኮከብ ሆቴሎች በሳምንት በአማካይ እስከ አምስትመቶ ኪሎግራም የዓሣ ምርት በውጭ ምንዛሬ ከውጭ ያስገባሉ፡፡
ሚኒስትሩ እንዳሉት በጋምቤላ ክልል በባሮና አኮቦ ተወዳዳሪ የሆነ አንዱ እስከ 150ኪሎ ግራም የሚመዝን ዓሣ ይገኛል፡፡ ሚኒስቴሩ ይሄን ሀብት ከማስገር ጀምሮ ተጠቃሚውጋ እስከሚደርስ አራትና አምስት ዘርፎች ባለው ሂደት የሚከናወን ቴክኖሎጂ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ለመግባት ቅድመሁኔታዎች አመቻችቷል፡፡ የቴክኖሎጂ እገዛው እስከ 20ሺ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ እድል እንደሚፈጥርና በቢሊዮን የሚቆጠር ገቢ እንደሚያስገኝም በጥናት ተረጋግጧል፡፡ ሚኒስቴሩ ከፌደራልና ከልሉ አስተዳደር ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን ከዘርፉ ሀብት ለማመንጨት ወደሥራው የሚገባበትን ቅድመ ሁኔታ አመቻችቷል፡፡
የአፋር ክልል ሴቶችን በቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ ከክልሉ ሴቶች ጋር ውይይት አድርጎ ፍላጎታቸውን መሠረት ያደረገ ቴክኖሎጂ ለመተግበር የመለየት ሥራ ተሰርቷል፡፡ ያወያያቸው የክልሉ ሴቶች ቅድሚያ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ወጭ ቆጣቢ የምግብ ማብሰያ እና የወተት ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂ ለመስራት ዝግጅት አድርጓል፡፡ በቀን ከፍተኛ ቁጥር የሚያስተናግደው ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አሰራሩን በማዘመን የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት እንዲያስችለው ሙሉ ለሙሉ «ዲጂታላይዝድ» ወይም በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልገሎት እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ ሚኒስቴሩ በትምህርት ቤቶች በተደጋጋሚ የሚነሳው የቤተሙከራ አጠቃቀም ችግርን ለመቅረፍም ተማሪዎች በንድፈሀሳብ የተማሩትን በተግባር በቤተሙከራ ውስጥ እንዲሰሩ ቤተሙከራ ማዕከልም አዘጋጅቷል፡፡
የዱር እንስሳትን ከተለያዩ ችግር ለመታደግ የሚያስችል፣የቱሪዝም ዘርፉን የሚደግፍ፣የፀረአረም ርጭት በሰው አልባ አውሮፕላን ለማከናወን የሚያስችልና ሌሎችም በቴክኖሎጂ የተደገፉ ሥራዎች ሚኒስቴሩ ከሰራቸው መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ሚኒስቴሩ የምርምር ሥራዎችንም በመደገፍ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመስራት ላይ ሲሆን፣እስካሁንም ስምንት ያህል የምርምር ሥራዎችን አስመርቋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ በቆሎን ለሚያጠቃ በሽታ በምርምር የተገኘው መፍትሄ እና ለመንገድ ሥራ የሚውል እንዲሁም ቆሻሻ ውሃን በማጣራት መልሶ መጠቀም ላይ ያተኮሩ የምርምር ውጤቶች ይጠቀሳሉ፡፡
ሚኒስትሩ እንደተናገሩት መስሪያቤታቸው በሚገኝበት አካባቢ የክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ለመገንባት እንቅስቃሴ ቢያደርግም እንዳሰበው አልታሳካለትም፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተሰጠው ቦታ ላይ የሚገኘው ተቋም ቦታውን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ያቀደውን ለመፈፀም አልቻለም፡፡ ከቦታው ለሚነሳው ተቋም ከፍተኛ የሆነ ካሳ እንደሚሰጠው ቢነገርም ተቋሙ ሊነሳ ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ የሚገነባው የማበልፀጊያ ማዕከል ትልቅ ተግባር የሚከናወንበት እንደሆነም ገልፀዋል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለጉዳዩ እልባት እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡
ሚኒስቴሩ «ከእርምጃ ወደሩጫ» በሚል መሪ ሀሳብ ከሶስት አመታት በፊት መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ የተገኙት ውጤቶች በአጭር ጊዜያቶች በተደረጉት እንቅስቃሴዎች መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሰው ኃይል አቅሙን ለማጠናከርም በተለያየ የትምህርት ደረጃ ባለሙያዎችን ለማፍራት ውጭ ሀገር ልኮ በማስተማር ላይ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡በህብረተሰቡ ዘንድ ለቴክኖሎጂ ያለው አመለካከት መቀየር እንዳለበት የገለፁት ሚኒስትሩ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በስፋት መከናወን እንዳለበትና ቴክኖሎጂን ከማፍለቅ ጎን ለጎን ግንዛቤ የመፍጠር ተግባር እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡

 ለምለም መንግሥቱ  

Published in ማህበራዊ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ በአገሪቱ ልዩ ልዩ ክፍሎች በመዘዋወር ከዜጎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ አገሪቱ ካጋጠማት ዘርፈ ብዙ ቀውስ ለማገገም የተለያዩ መፍትሄ እርምጃዎችንም በመወሰድ ላይ ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገር ውስጥ ላደረጉዋቸው ጉዞዎችና ውይይቶች ባሻገር ከምስራቅ አፍሪካ አገራት መሪዎች ጋር እጅ ለእጅ መጨባበጥ ከጀመሩም ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡ የተጨባበጡ እጆችም ጭብጥ ያለው ተግባር እያሳዩ ነው፡፡ የተበተኑ ሃሳቦችንም በማሰባሰብ የአንድነት መንፈስ በምስራቅ አፍሪካ እንዲጎለብት በርካታ አዎንታዊ ትርጉም ያላቸው ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው፡፡ ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩን የአገር ውስጥና የውጭ ጉብኝት ቀጣይ የቤት ሥራዎችን አስመልክቶ ምሁራን ሃሳባቸውን ይሰነዝራሉ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግና አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ፤ ከዲፕሎማሲ አኳያ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተቀባይነት የጎላ እንደሆነ፣ በሳል አተያይና አካሄድ እየተከተሉ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በአገር ውስጥ እየተከናወነ ያለው ሥራ በውጭው ዓለም የራሱን ነፀብራቅ እየፈጠረ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገር ውስጥ ከህዝቡ ጋር ተቀራርበው ሃሳብ መቀበላቸው ስኬታማ እያደረጋቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ ካላት ተፅዕኖ ፈጣሪነት አኳያም በርካታ አገራት በትብብር መሥራት ይፈልጋሉ፤ በፍጥነትም ምላሽ በመስጠት ላይ ናቸው ይላሉ፡፡
ወቅታዊ የምስራቅ አፍሪካ ችግሮችን በማለዘብም ሆነ መፍትሄ በመስጠት ኢትዮጵያ ቀዳሚ እና ታላቅ አገር ናት የሚሉት ዶክተር ሲሳይ፤ በማንኛውም መመዘኛ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዞ እና የሥራ ጉብኝት ታላቅ ድጋፍ ያለው ነው የሚል አቋም አላቸው፡፡
ዶክተር ሲሳይ በአሁኑ ወቅት ከጅቡቲ እና ሱዳን ጋር ወደቦችን በጋራ ለማልማት የተፈረሙት ሰነዶች በህግ መነጽር ጥልቅ ትርጉም ያላቸውና የአገራቱን የጋራ ዕጣ ፋንታ በጋራ ለመወሰን የሚያስችል ውሳኔ ነው፡፡ ኢትዮጵያም የብልህ አመራር፤ የጠንካራ ዲፕሎማሲና ምጣኔ ሃብታዊ መሠረቱ የጠነከረ ወዳጅነት እየፈጠረች ስለመሆኑ ማሳያ ናቸው፡፡ ስምምነቶቹ ህጋዊ መሰረት ያላቸውና የጋራ ግንኙነቱን ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ የሚያኖሩ ሲሆኑ፤ በተለይ ደግሞ ከሱዳን እና ኬንያ ጋር የተደረሰው ውሳኔ በእጅጉ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ያስረዳሉ፡፡
ኢትዮጵያ በቀጣይም በርካታ የቤት ሥራዎች እንደሚጠብቃት የሚናገሩት ዶክተር ሲሳይ፤ በሱዳን እና በኬንያ በህግ ከለላ ስር የነበሩ ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን ያደንቁታል፡፡ የአንድ አገር መሪ ለዜጎቹ ሲል መቆርቆርም ሆነ መደራደር አለበት፡፡ ነገር ግን ይህ እስካሁን አገሪቱን ይመሩ ከነበሩ መሪዎች ያልተሞከረና ለየት ያለ በመሆኑ ትልቅ ጭብጥ ነው ይላሉ፡፡ በሌላውም ዓለም በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከእስር እንዲፈቱ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቱ መጠናከር አለበት፡፡ ከዚህም ባሻገር አገሪቱ ያጋጠማትን ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ ለማስተካከል የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት በሚያስችሉ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲና ኢንቨስትመንት ላይ ሊያተኩሩ ይገባል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገራትም ማቅናታቸው እንደማይቀር የሚጠቁሙት ዶክተር ሲሳይ፤ የኢትዮጵያ ዜጎች በሠላማዊ መንገድ ሰርተው ስለሚኖሩበት ሁኔታ ሊመክሩ ይገባል፡፡ ከምንም በላይ ግን በአገሪቱ ውስጥ ላሉ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ የጉብኝታቸውም አነሳስና አካሄድም የሚደነቅና ትክክለኛ ውሳኔ ሲሆን፤ በህግ እይታም ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ብሎም በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ትርፋማ የሚያደርግ እንደሆነ ነው የሚያብራሩት፡፡
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት አቶ ሞላ ዋሴ በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ላይ ሊኖራት የሚገባትን ሚና ለማሳደግ የጀመሩት ጥረት ‹‹አዎንታዊ ሚና አለው›› ሲሉ የዶክተር ሲሳይን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡
እንደ አቶ ሞላ ገለፃ፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው የምጣኔ ሀብት የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ ለማጠናከር የተጀመረው ጥረት በውጪውም ሆነ በአገር ውስጥ የሚሰጠው ትርጉም ከፍያለና ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ላይ የነበራትን ሚና ለማስቀጠል ሰፊ ዕድል የሚሰጣት ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ከሱዳን እና ጅቡቲ ጋር ወደቦችን በጋራ በማልማት፤ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመረው ጥረት የሚደገፍ ሃሳብ ነው፡፡ ይህም ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካም ሆነ በሌሎች ዓለማት በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የሚኖራትን ሚና በእጅጉ ያሳድገዋል፡፡ ከዚህም በዘለለ ከተለያዩ አገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ኢንቨስተሮች እና የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ምርታቸውን በፈለጉት ጊዜ ወደተፈለገው አቅጣጫ ለማንቀሳቀስ የሚኖረው ፋይዳ ብዙ ነው፡፡
እንደ ምጣኔ ሃብት ባለሙያው ከሆነ፤ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ እየተጫወተች ያለው ሚና ሌሎች አፍሪካ አገራትንም የሚቀሰቅስና አገሪቱን በተሻለ የዕድገት ደረጃ ላይ ሊያስቀምጣት የሚችል እንደሆነ ነው የሚናገሩት፡፡
አገሪቱ በአሁኑ ወቅት በምስራቅ አፍሪካም ሆነ በአገር ውስጥ በሁሉም መስኮች እየተከተለችው ያለው ዘርፈ ብዙ ዲፕሎማሲና አሠራር የሚደነቅ እንደሆነ በመጠቆም፤ በተለይም የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን ማበረታታት፣ የውጭ አገር ባለሃብቶችን መሳብና ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገቱን ማስቀጠልና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ በማጠናከር በምስራቅ አፍሪካ የገበያ መዳረሻዎችን ላይ በሰፊው ማማተር ይገባታል ይላሉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው
የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አቶ ገዛኸኝ በርሔ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገር ውስጥ እና የምስራቅ አፍሪካ ጉብኝት ብዙ ትርጉም ያለው እንደሆነ በመግለፅ በምሁራኑ ሃሳብ ይስማማሉ፡፡ በተለይም ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ ያሉትን አገራት በማግባባትና ተፅዕኖ በመፍጠር ረገድ ኢትዮጵያ የነበራትን ሚና ለማስቀጠል አያሌ ፋይዳዎች አሉት፡፡ ጉብኝቱ በምስራቅ አፍሪካ ያለውን ተግባቦት በሚገባ የሚያጠናክርና በአንዳንድ አጋጣሚዎች ችግሮች እንኳን ቢፈጠሩ ሊጠገን የሚችልበት የስትራቴጂካዊ የተግባቦት አካሄድና ሰፊ ዕድልን የሚፈጥር እንደሆነ ያስገነዝባሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአገር ውስጥ ጀምረው በርካታ የጉብኝት መዳረሻዎቻቸውን በምስራቅ አፍሪካ ማድረጋቸው ተግባራቸው ከንግግር ባለፈ እውነተኛ ወዳጅ ለማፍራት አመቺ መደላድል እንደሚሆን ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ፡፡
እንደ አቶ ገዛኸኝ ገለፃ ከሆነ፤ በአሁኑ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመረው የምስራቅ አፍሪካ ጉበኝት በሌሎች አገራትም እንደሁኔታው መቀጠል ያለበት ጉዳይ ሲሆን በኢትዮጵያ እና በጋራ ጥቅሞች ላይ ጠንካራ የማግባባት ስልትና ዲፕሎማሲ መከተል እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ መሰል ጉብኝቶችና ግንኙነቶችም ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ችግሮችን በአፋጣኝ እልባት ለመስጠት ብሎም መፃዒ ዕድል ላይ በሰፊው ለመምከርም ላቅ ያለ መሰረት የሚጥል ነው፡፡
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑትና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ኀሳቡ ተስፋ በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በምስራቅ አፍሪካ አገራት ያካሄዷቸው ጉብኝቶች በዓለም አቀፍ የግንኙነት ስሌትም ሆነ በውጤታማ ዲፕሎማሲ ቀመር መሰረት ሲመዘን ሚዛን የሚደፋ መሆኑን ያብራራሉ፡፡ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መሰረት ለጎረቤት አገራት የሚሰጠው ትኩረትም ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህም አኳያ እየተከናወኑ ያሉት ግንኙነቶች የአገሪቱን ፍላጎት ያስቀደሙና የአገሬውን ህዝብ ጥያቄ ማዕከል ያደረጉ ናቸው ይላሉ፡፡
እንደ አቶ ኀሳቡ ገለፃ፤ ኢትዮጵያ በርካታ የውጭ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ የምታስገባው በጅቡቲ ወደብ ተጠቅማ ሲሆን፤ይህም በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ትልቅ ትኩረት ሊሰጣት የምትገባ አገር በመሆኗ የመጀመሪያው የውጭ አገር ጉብኝቱ በጅቡቲ መሆኑ ተገቢና የሚደነቅ ነው፡፡
በሱዳን የተካሄደው ጉብኘትም በፖለቲካዊ ዳራ ሲታይ እጅጉን ጠቃሚና በቀጣይም ሊጠናከር የሚገባ እንደሆነ ነው የሚጠቁሙት አቶ ኀሳቡ፡፡ በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጉዳይ በሁለቱ አገራት የውይይት ወቅት እንደ አጀንዳ ሆኖ መነሳቱ አሁንም ቢሆን ሱዳን ያላትን የማያወላዳ አቋም የሚያሳይ ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ መርህ የኢትዮጵያ አሸናፊነት እየጎላ ስለመምጣቱ እና ወዳጆችን ለማፍራት የዘረጋችው መረብ የምትፈልገውን ነገር እያጠመደላት ስለመሆኑ ማሳያ ነው ይላሉ፡፡
አቶ ኀሳቡ የሱዳኑ ጉብኝት የሁለቱን አገራት ግንኙኑት እንዲጠናከር ከመምከር በዘለለ ለግብፅም አንዳች መልዕክት እንዳለው ነው የሚያብራሩት፡፡ በተለይም ደግሞ ግብፅ በህዳሴው ግድብ ላይ ለብቻዋ የምታራምደው ግትር ሃሳብ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ እየተሸነፈ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን ሃያልነትም እንድትረዳ ትልቅ አጋጣሚ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
እንደ አቶ ሃሳቡ ገለፃ በኬኒያ የተደረገው ጉብኝትም ሁለቱ አገራት የቆየ ወዳጅነታቸውን ለማጠናከርና የላሙ ወደብን በጋራ ለማልማት ከዓመታት በፊት የተፈራረሙትን ስምምነቶች በሰፊው እንዲፈትሹ ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡
አቶ ሃሳቡ ቀደም ሲል በነበሩት የአገር መሪዎች ያልተሞከረውና በአሁኑ ወቅት ብቻ እንደ ትልቅ አጀንዳ ተደርጎ የተወሰደው በኬኒያ እና ሱዳን በህግ ጥላ ስር ያሉ የኢትዮጵያ ዜጎች ከእስር እንዲፈቱ ከስምምነት ላይ መደረሱ የጠንካራ ዲፕሎማሲ ማሳያ እንደሆነም ይጠቁማሉ፡፡
ጎረቤት አገራት በስጋትም ሆነ በስኬት የሚገጥማቸው ጉዳይ ሁሉ በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጥረው አዎንታዊ ይሁን አሉታዊ ጫና ከፍተኛ በመሆኑ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን መሰረት በማድረግ ጠንካራ ድርድሮችና ግንኙነቶች መደረግ አለባቸው የሚሉት አቶ ሃሳቡ፤ በቀጣይም የአቻ ግንኙነቱን በበለጠ ለማጠናከርና የኢትዮጵያን ጥቅሞች ባስጠበቀ መልኩ ድርድሮችና ውይይቶች መካሄድ እንደሚኖርባቸው ያስገነዝባሉ፡፡

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

 

 

 

Published in ፖለቲካ

በተለያዩ ቀለማትና ዲዛይን የተሰሩት የአልጋ፣ የጠረጴዛና የተለያዩ አልባሳት እይታን በሚስብ መልኩ ተደርድረዋል፡፡ምርቱ በፎቶግራፍም ለእይታ ከፍ ብሎ ተሰቅሏል፡፡የቀረበው የሀገር ባህል ሥራ ምርቱ ትኩረትን ይስባል፡፡ደንበኛን ለመሳብ የተደረገውንም ጥረት ያሳያል፡፡ጥረት የታከለበት የእጅ ጥበብ አልባሳት ሥራ በተፈጥሮ እጆችዋን ባጣችው በወይዘሪት ዓለምነሽ ያሲን የቀረበ መሆኑ ደግሞ እንዴት ተሰራ በሚል የተለየ እይታ እንዲኖረኝ አድርጎኛል፡፡
«ዘላቂነት ያለው የገበያ ትስስር ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት መሠረት ነው»በሚል መሪ ሀሳብ ከሚያዝያ 24 እስከ 30/2010 ዓ.ም በተካሄደው ሀገር አቀፍ የሞዴል ኢንተርፕራይዞች ባዛርና ኤግዚቢሽን ላይ የእጅ ሥራ ውጤቶችዋን ይዛ የቀረበችው ወይዘሪት ዓለምነሽ ከልጅነቷ የጀመረችው የጥልፍ ሥራ የሙያ ባለቤት አድርጓታል፡፡
ወይዘሪት ዓለምነሽ ሥለስራዋ እንዳጫወተችኝ የጥልፍ ሥራዎችን እየሰራች ለገበያ የምታቀርበው በቤቷ ውስጥ ነበር፡፡ገዢ በማፈላለግ ምርቷን ሸጣ ከምታገኘው ገቢም «ሁሉን አልፋ» በተባለው ሴት አካል ጉዳተኞች ብድርና ቁጠባ ማህበር በየወሩ አስር ብር ትቆጥባለች፡፡ ሥራዋን ያዩ ሁሉ ሲያበረታቷት፣ ቁጠባዋም ሲያድግ አደባባይ ለመውጣት አቅም አገኘች፡፡
ከ«ሁሉን አልፋ»ማህበር ባገኘችው የገንዘብ ብድር በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ተደራጅታ ሥራዋን ለአደባባይ አበቃች፡፡ መንግሥትም ጥረቷን አይቶ በአራዳ ክፍለከተማ ወረዳ ሰባት ግንፍሌ ሼድ (ማኑፋክቸሪንግ ግቢ)ውስጥ ማምረቻ ሱቅ ሰጣት፡፡ ላለፉት አምስት አመታትም በተሰጣት ማምረቻ ሱቅ ውስጥ እየሰራች ትገኛለች፡፡ በተለያየ ጊዜም የሞዴል ኢንተርፕራይዞች ማበረታቻ ሽልማቶችን አግኝታለች፡፡
ወይዘሮ ዓለምነሽ የተሰጣት የመስሪያ ቦታ ለሽያጭ ምቹ ባለመሆኑ ምርቶችዋን በተለያየ መንገድ ነው የምትሸጠው፡፡ አንዳንድ ሰዎች በእቁብ ገንዘብ እያሰባሰቡ በብዛት ይወስዱላታል፡፡ገበያ ለማግኘት ባዛርና ኤግዚቢሽን የተሻለ እንደሆነ ትገልፃለች፡፡እርሷ እንዳለችው በእለቱ ገበያ ባታገኝም ሌላ ጊዜ ደንበኞች የማግኘት አጋጣሚ ይፈጥርላታል፡፡በዚህ መልኩ ምርቷን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ብትሆንም፣ የልፋቷን ያህል የምትፈልገው ደረጃ ለመድረስ አለመቻሏ ቁጭት ውስጥ ከቷታል፡፡ሥራዋ በማሽን የታገዘ ባለመሆኑ አድካሚ ነው፤ በብዛት እንዳታመ ርትም አድርጓታል፡፡
ማሽን በብድር ለመግዛት አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም የሚጠይቀውን የብድር ዋስትና አታሟላም፡፡ ከሌሎች ጋር በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅታ በጠለፋ ዋስትና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዳትሆን በአንድ ላይ መዝለቁ አስተማማኝ ባለመሆኑ ችግር ፈጥሮባታል፡፡ በትርፋማነቱ የተሻለ ነው በምትለው በቆዳ ማምረት ላይ ለመሰማራት ፍላጎቱ ቢኖራትም የእጅ ጉዳቷ እንዳገዳት ትናገራለች፡፡የቆዳ ሥራው ከጨርቃጨርቁ የበለጠ ጉልበት እንደሚጠይቅ ገልፃለች፡፡
ወይዘሪት ዓለምነሽ ሥራዋ ከፍተኛ ለውጥ እያስገኘላት ባለመሆኑ ከምትወደው ሙያ ለመውጣት እያሰበች ነው፡፡በአሁኑ ጊዜ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በርቀት በሚሰጠው ትምህርት የህግ ትምህርት እየተከታተለች እንደምትገኝና ዘንድሮ እንደምት ጨርስም ገልፃልኛለች፡፡ ወደፊትም በተማረችው ሙያ ለመስራት ማቀዷን ትናገራለች፡፡
ከትግራይ ክልል ከአክሱም ከተማ የተለያዩ የባህል አልባሳትን ይዛ በኤግዚቢሽኑ ላይ የቀረበችው ሌላዋ ሞዴል ኢንተርፕራይዝ ወይዘሪት ዓለምነሽ ፋንታ እንዳጫወተኝ የሀገር ባህል ልብስ ሽያጭ የጀመረችው በጎዳና ላይ ሲሆን፣ከአክሱም አዲስ አበባ ከተማ በማምጣት በጎዳና ላይ ትሸጥ ነበር፡፡ሱቅ ከፍታ ለመሸጥ የሚያስችል ገንዘብ አልነበራትም፡፡ የገንዘብ ችግሯን ለማቃለል በሰው ቤት ተቀጥራ ለአራት አመታት ሰርታለች፡፡ ያጠራቀመችውንና ከተለያዩ ሰዎች በብድር ባገኘችው 30ሺ ብር ነው ወደ ንግድ ሥራ የገባችው፡፡ከዚህ ሁሉ ጥረት በኋላ አክሱም ከተማ ላይ በስሟ የከፈተችውን የባህል አልባሳት መሸጫ ሱቅ ተከራይታ መስራት ጀመረች፡፡ ሞዴል ሆና በኤግዚቢሽኑ ላይ መሳተፏ ነገን የተሻለ እንድታስብ አስችሏታል፡፡በአሁኑ ጊዜ ካፒታሏ ወደ50 ሺ ብር ደርሷል፡፡
ወይዘሪት ዓለምነሽ እንደነገረችኝ ባዛርና ኤግዚቢሽን በሚካሄድበት ሁሉ የመሳተፍ ዕድል ማግኘቷ የገበያ ትስስር ፈጥሮላታል፡፡ሱቅ ውስጥ ከምታገኘው ገበያ የተሻለ መሆኑንም ትናገራለች፡፡ ወይዘሪት ዓለምነሽ የጥልፍ ችሎታ እንዳላትና የአንዳንድ አልባሳቶችዋ ጥልፍም የራስዋ መሆናቸውን ገልፃለች፡፡ወደፊት ከሀገር ውጭም የባህል አልባሳትን በማቅረብ ከፍ ወዳለ ደረጃ ለመሸጋገር ነው እቅዷ፡፡
በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት ውስጥ የኤሌክትሪክ የእንጀራ፣የዳቦ መጋገሪያዎችና የምግብ ማብሰያ ምጣድና ምድጃዎችን በመስራትና ለገበያ በማቅረብ ላይ የሚገኙት አቶ ደምሴ ጎበዜ ወደዚህ ሥራ የገቡት ከአምስት አመት በፊት ከግለሰብ ባገኙት ሶስት ሺህ ብር ብድር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ለሰባት ሰዎችም የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡በልደታ ክፍለ ከተማ ቀበሌ ዜሮ አምስት በተሰጣቸው የማምረቻና የመሸጫ ሼድ ውስጥ በመስራት ላይ ናቸው፡፡ቦታው ጠባብ በመሆኑ ብዛት ያለው የሰው ኃይል ለመቅጠርና ሰፊ ገበያ ለማስተናገድ ስላላስቻላቸው ሰፊ ቦታ እንዲሰጣቸው በማመልከቻ የሚኖሩበትን ቀበሌ ጠይቀዋል፡፡
አቶ ደምሴ ወደዚህ ሥራ ከመግባ ታቸው በፊት በተለያዩ ሥራዎች ላይ ቢቆዩም ከሌሎች ባለሙያዎች የኤሌክ ትሪክ ሙያውን እንደቀሰሙና በጥረታ ቸው ሥራውን ለመስራት መብቃታቸውን ይገልፃሉ፡፡ ጥረታቸው ለውጤት እንዳበቃ ቸውም ተናግረዋል፡፡ ሥራቸውን ለማሳደግም ቁጠባ በመቆጠብ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ወይዘሪት ዓለምነሽ ፋንታ


ለሁለተኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው ሀገር አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ ከዘጠኝ ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ201 በላይ የሚሆኑ ሞዴል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ተሳትፈዋል፡፡ ያነጋገር ኳቸው አብዛኞቹ ኢንተርፕራ ይዞች ከአነስተኛ ካፒታል ተነስተው ነው ሞዴል ለመሆን የበቁት፡፡ ወደከፍተኛ ኢንዱስትሪ ተሸጋግረው የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ያላቸው ፍላጎትም ከፍተኛ ነው፡፡ ባዛርና ኤግዚቢ ሽኑ ለገበያ ትስስር እንደሚጠቅ ማቸውም ገልፀዋል፡፡
የመሸጫና የማምረቻ ቦታ አለመሟላት፣ የብድር አገልግሎቱም ተጠቃሚ እንዳላደረጋቸው በነበረኝ ቆይታ ገልፀውልኛል፡፡ በዕለቱም ምርትና አገልግሎታቸውን የሚዘረጉበት ቦታ አጥተው በጊዜ ወደሥራ ያልገቡ አንዳንድ ኢንተርፕራይዞችን አስተውያለሁ፡፡
ሞዴል ኢንተርፕራይዞቹ ላነሱት የብድር አገልግሎት፣የማምረቻና የመሸጫ ቦታ ጥያቄ በኤግዚቢሽኑ መክፈቻ ላይ የነበሩትን የፌዴራል ከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ኩሞን ጠይቄያቸው ምላሽ ሰጥተውኛል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ስለብድር አሰጣጥ እንዳስረዱት መንግሥት ከሚያደርጋቸው ድጋፎች ውስጥ አንዱ የብድር አገልግሎት ማመቻቸት ነው፡፡በዚሁ መሠረትም ሀብት የሌላቸው መደበኛ የሥራ ዕድል ፈጠራ ቅድመ ብድር 20 በመቶ መቆጠብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ ተጠቃሚዎች ከሆኑ ደግሞ 10 በመቶ መቆጠብ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህን ካሟሉ በኃላ የሥራ ዕቅድ(ቢዝነስ ፕላን) አዘጋጅተው ያቀርባሉ፡፡በዚህ ሂደት ውስጥ ላለፉት ሙያዊ ክህሎት ስልጠናና መስፈርቱን ላሟሉት ብድር ይሰጣል፡፡
የብድር አሰጣጡም በሁለት መንገድ ይፈፀማል፡፡ የማኑፋክቸሪንግ የንግድ ዘርፍ ከሆነና ካፒታሉም ከፍተኛ ከሆነ ተጨማሪ ዋስትና ይጠየቃል፡፡ለአነስተኛ ብድር ግን የተደራጁ አባላት እርስ በርስ ዋስ በመሆን ወይም የጠለፋ ዋስትና በሚባለው አሰራር ይስተናገዳሉ፡፡የብድር አገልግሎቱን በተናጠል ከሚጠይቁት ለተደራጁት ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ይህ የሚሆነው ውስን የሆነውን ሀብት በፍትሐዊነት ለማዳረስ ሲባል ሲሆን፣ለተደራጁት የዋስትና ጥያቄ ችግርን ለማቃለልም ይረዳል፡፡
የብድር አገልግሎት አሰራር በዚህ መንገድ ቢፈፀምም ክፍተቶች እንዳሉበት ዋና ዳይሬክተሩ አልሸሸጉም፡፡ «የብድር አገልግሎቱ ግልፅ የሆነ አሰራር ቢኖረውም መሬት ላይ ያለው እውነታ የተለያየ ነው፡፡ ለዋስትና የቤት ካርታና የመኪና ሊብሬ ይጠየቃል፡፡ አሰራሩ ከፍተኛ ማነቆ መፍጠሩን በበጀት አመቱ የስድስት ወር የሥራ ግምገማ ለይተን መስተካከል እንዳለበት ከአመራሩ ጋር መግባባት ላይ ደርሰናል» በማለት ገልፀዋል፡ ፡ከፍተኛ አመራሩ አቅጣጫ ማስቀመጡንና አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም የነበረውን ክፍተት ተቀብሎ በመመሪያው መሠረት ለመፈፀም በደብዳቤ ለኤጀንሲው ማሳወቁን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ ለውጡ በተግባር መፈፀሙን መከታተልና እንዲፈፀም የማድረግ ሥራ በተከታታይነት ሊተገበር እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ዘነበ የመስሪያና የመሸጫ ቦታን በተመለከተ እንደገለፁት ውስን የሆነውን ሀብት ለሁሉም ማዳረስ ባለመቻሉ ፍላጎትና አቅርቦት አልተጣጣመም፡፡ ከጥቃቅንና አነስተኛ ስትራቴጂ ውጭ ያለውን አጠቃቀም ባለማስተካከል የተፈጠረውን ችግርም ኤጀንሲው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ገምግሟል፡፡ ካፒታላቸው እየታየ ወደ መካከለኛና ከፍተኛ መሸጋገር ያለባቸውን ባለማሸጋገር፣ ተሸጋግረውም የመስሪያና መሸጫ ቦታውን እንዲለቅቁ ባለማድረግ የተፈጠረው ክፍተት ተስተካክሎ ለተተኪዎች እንዲሰጥ የማድረግ እርምጃ ተጀምሯል፡፡
በኤግዚቢሽን ላይ ቦታ ካለማግኘት ጋር ተያይዞ የነበረውን ክፍተት በተመለከተም ዋና ዳይሬከተሩ እንዳስረዱት ኤግዚቢሽን ላይ የመቅረብ ፍላጎት እየጨመረ ነው፡፡ በዕለቱም ቦታ ከተዘጋጀላቸው ተጨማሪ ኢንተርፕራይዞች መቅረባቸው ክፍተቱን ፈጥሯል፡፡ ኤጀንሲው የቦታ ችግርን ለመቅረፍና ጊዜያትን ጠብቆ የሚካሄድ ባዛርና ኤግዚቢሽን ለማስቀረት ከከተማ አስተዳደሩ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ባገኘው 3ሺ400ካሬ ሜትር ላይ ደረጃውን የጠበቀ የገበያ ማዕከል ለመገንባት አቅዷል፡፡የመስሪያ በጀት እንደተፈቀደ ወደ ግንባታ ሥራው እንደሚገባም ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
የሥራ ዕድል ፈጠራ አምስት የዕድገት ተኮር መስኮች ያሉት ሲሆን፣እነርሱም ማኑፋከቸሪንግ፣ የከተማ ግብርና፣ ኮንስትራክሽን ንግድና አገልግሎት ናቸው፡፡ በነዚህ ዘርፎች ላይ በግልም በቡድንም ተደራጅቶ በመስራት ዜጎች ሀብት እንዲፈጥሩ የሚደረገው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን የተለዩ ክፍተቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ለስኬት ማብቃት ይጠበቃል፡፡

ለምለም መንግሥቱ 

Published in ኢኮኖሚ

አወዛጋቢው ሰው አወዛጋቢ ውሳኔዎችን በመወሰን ዓለምን ማነጋገራቸውን ቀጥለውበታል፡፡ ቢሊየነሩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካን እ.ኤ.አ በ2015 በኢራንና በስድስቱ ኃያላን አገሮች (አሜሪካ፣ ሩስያ፣ ቻይና፣ ብሪታኒያ፣ ጀርመንና ፈረንሳይ) መካከል ከተፈረመው የኢራን የኑክሌር ስምምነት አስወጥተዋታል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ኢራንና ስድስቱ ኃያላን አገራት የተፈራረሙትን ስምምነት የተቃወሙት ገና በፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተመረጡም ስምምነቱን እንደሚሽሩት ተናግረው ነበር፡፡ ይኸው ጊዜው ደረሰላቸውና ‹‹አሜሪካንና አሜሪካውያንን ያሳፈረ የምንጊዜውም መጥፎው ስምምነት›› እያሉ ያብጠለጠሉትን ስምምነት ሰረዙት፡፡
ፕሬዚዳንቱ አገራቸው ከስምምነቱ ስለመውጣቷ በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹አሜሪካ ከኢራን የኑክሌር ስምምነት የወጣችው ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት እንዳትሆን የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር ነው›› ብለዋል፡፡ እንደተለመደው የኢራንን መንግሥት በወረፉበት መግለጫቸው፣ ስምምነቱ ኢራንን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት እንድትሆን እድል የሚሰጣት እንጂ ወረቀት ላይ እንደተፃፈው ኢራን ከአውዳሚ የጦር መሳሪያ ባለቤትነት የሚያግዳት እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ቀደም ብለውም ቢሆን ስምምነቱን እንደሚሽሩት በተደጋጋሚ ተናግረው የነበረ ቢሆንም የስምምነቱ ፈራሚ የሆኑ የአውሮፓ አጋሮቻቸውና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፕሬዚዳንቱ አሜሪካን ከስምምነቱ እንዳያስወጧት በተደጋጋሚ ተማፅነዋቸው ስለነበር ቃላቸውን ሊያጥፉ ይችላሉ ብሎ ተስፋ ያደረገው ሰው ብዙ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሰውዬው ‹‹ቃል የገባሁትን ሁሉ የምፈፅም ሰው ነኝ›› በማለት አወዛጋቢውን ውሳኔያቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
ትራምፕ ስምምነቱ ኢራንን ከኑክሌር ማበልጸግ ተግባሯ የሚገታ ሳይሆን እንዲያውም ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ባሊስቲክ ሚሳይሎችን ከማምረት የሚያግዳት አይደለም ብለው ያምናሉ፡፡ በተጨማሪም ስምምነቱ ኢራን በውጭ አገራት ባንኮች ያላትንና እንዳይንቀሳቀስ ታግዶባት የነበረውን 100 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ እንዲለቀቅላት ስላደረገ ኢራን ገንዘቡን ሽብርተኞችን ለመደገፍ፣ የጦር መሳሪያ ለመግዛት እንዲሁም አክራሪነትን ለማስፋፋት ተጠቅ ማበታለች፤ ደካማና ለኢራን ጠቃሚ የሆነውን ስምምነት እንኳ ማክበር ተስኗታል ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
አገራቸው ከስምምነቱ ስለመውጣቷ በሰጡት መግለጫም የተናገሩት ይህንኑ ነው፡፡ ‹‹ስምምቱ ከተፈረመ ወዲህ ኢራን ወታደራዊ በጀቷን በ40 በመቶ ከፍ በማድረግ የኑክሌር ጦር መሳሪያ መገንባቷን ገፍታበታለች፤ ስምምነቱ ደካማና ኢራንን ብቻ የሚጠቅም ቢሆንም እንኳ ኢራን ይህንንም ማክበር አልቻለችም›› ብለዋል፡፡
የትራምፕን ውሳኔ ተከትሎ የስምምነቱ ፈራሚ የሆኑ አገራት መሪዎች ስለጉዳዩ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ኢራን ፕሬዚዳንት ሀሰን ሮሐኒ ከትራምፕ ውሳኔ በኋላ በሰጡት መግለጫ፣ ውሳኔውን በፅኑ ኮንነውታል፡፡ ‹‹የትራምፕ ውሳኔ ተቀባይነት ስለሌለው ቴህራን ከሌሎቹ የስምምነቱ ፈራሚ አገራት ጋር በጋራ ትሰራለች›› ብለዋል፡፡ የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሚኒ በበኩላቸው፣ ‹‹ከመጀመሪያው ‹አሜሪካንን አትመኑ› ብዬ ተናግሬ ነበር›› በማለት ለውሳኔው ያላቸውን ተቃውሞ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ ብሪታኒያን፣ ፈረንሳይንና ጀርመንንም እንደማያምኑ ገልጸው፣ ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በፊት ከነዚህ የአውሮፓ አገራት ማረጋገጫ ማግኘት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
‹‹ስምምነቱን ለማክበር ከተፈለገ ከሌሎቹም አገራት ትክክለኛ ዋስትና ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ የሚናገሩት ሁሉ አይጨበጥም፤ ዛሬ ለአንድ ነገር ቃል ገብተው ነገ ደግሞ ቃላቸው ያጥፋሉ፤ ፈፅሞ አይታመኑም፤ ሀፍረትም አይሰማቸውም›› በማለት ምዕራባውያኑን ወርፈዋቸዋል፡፡
ባለፈው ወር ወደ ዋሽንግተን ዲ.ሲ በመሄድ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከኢራን የኑክሌር ስምምነት እንዳይወጡ ፕሬዚዳንቱን አግባብተዋቸው የነበሩት የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የትራምፕን ውሳኔ ‹‹ስህተት›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡
የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ደግሞ አሜሪካ ከስምምነቱ መውጣቷ እንዳሳዘናቸውና አገራቸው ብሪታኒያ ግን ከስምምነቱ የመውጣት ሃሳብ እንደሌላት ገልጸዋል፡፡ የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በበኩላቸው፣ ‹‹ኢራን የስምምነቱን ድንጋጌዎች እንድታከብር የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን›› ብለዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄይኮ ማስ፣ ‹‹ስምምነቱ ዓለምን ሰላምና ጸጥታ እንዲጠበቅ ያደረገ ነው፤ ጀርመን ከስምምነቱ ለመውጣት የሚያስገድድ ምንም ዓይነት ምክንያት አላገኘችም›› ብለዋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳዮችና የደህንነት ኃላፊዋ ፌደሪካ ሞግሪኒ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢራን ኑክሌር ስምምነትን እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ኃላፊዋ ከብራሰልስ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የአውሮፓ ኅብረት ስምምነቱ በተገቢው መልኩ እንዲተገበር ቁርጠኛ አቋም እንዳለውና ለዚህም ሙሉ ጥረቱን እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
ኅብረቱ ዓለም አቀፉ የኑክሌር ተቆጣጣሪ ተቋም በኢራን ያካሄዳቸውን ምልከታዎችና የምልከታ ዎቹን ሪፖርቶች እንደሚያምንና ኢራን ስምምነቱን እያከበረች ስለመሆኗ ተናግረዋል፡፡
ልክ እንደ አውሮፓ ኅብረት ሁሉ ቻይናም ስምምነቱ እንዲከበር የበኩሏን አስተዋፅዖ እንደምታደርግ ገልፃለች፡፡ በመካከለኛው ምስራቅ የቻይና ልዩ መልዕክተኛ ጎንግ ሺያዎሼንግ ኢራን ውስጥ በሰጡት መግለጫ፣ ስምምነቱ ሰላምና ማስፈን እንደቻለ ገልጸዋል፡፡ ዥኑዋ እንደዘገበው፣ ‹‹ውይይት ከአተካራና ፍጥጫ የተሻለ መንገድ ነው፤ ከስምምነቱ ከመውጣት ይልቅ ስምምነቱ እንዲከበርና እንዲተገበር ጥረት ማድረግ የተሻለ ነው›› ብለዋል፡፡
በሩስያ የላይኛው ምክር ቤት የመከላከያና ደህንነት ኮሚቴ ምክትል ሊቀ-መንበር የሆኑት የቭጌኒ ሴረብሬንኮቭ፣ የፕሬዚዳንት ትራምፕ ውሳኔ አሜሪካ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ለምታደርገው ውይይት መሰናክል ሊሆንባት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ‹‹ትራምፕ አሜሪካን ከስምምነቱ ቢያስወጧትም፣ ሩስያ ስምምነቱ እንዲተገበር ትሰራለች›› ብለዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ ሌሎቹ የሥምምነቱ ፈራሚ አገራት ስምምነቱን እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ጃፓንና አውስትራሊያም የትራምፕን ውሳኔ ተቃውመዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ማልኮም ተርንቡል ሁሉም ወገኖች ለውሳኔው የሚሰጡትን ምላሽ በተረጋጋ መንፈስ እንዲያስቡበት መክረዋል፡፡ የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታሮ ኮኖ፣ የትራምፕ ውሳኔ ኢራን ስምምነቱን ከማክበር የሚያግዳት እንደማይሆን አገራቸው ያላትን ተስፋ ገልፀዋል፡፡ ‹‹ሌሎቹ የሥምምነቱ ፈራሚ አገራት ጉዳዩን በበጎ ሁኔታ እንደሚያስቀጥሉት ተስፋ አለን›› ብለዋል፡፡
በሶርያ ጉዳይ ከኢራን ጋር አብራ እየሰራች ያለችው ቱርክም የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ውሳኔን ተቃውማለች፡፡ የፕሬዚዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶጋን ቃል አቀባይ ኢብራሂም ካሊን፣ ‹‹የአሜሪካ ውሳኔ የዓለምን ሰላምና መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥል ነው፤ ቱርክ የትኛውም አገር የኑክሌር ጦር መሳሪያ እንዲታጠቅ አትፈልግም›› ብለዋል፡፡ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ደግሞ ስምምነቱ ግልፅ በሆነና በተሟላ መልኩ ሊተገበር እንደሚገባ በመግለጫው አመልክቷል፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ አሜሪካ ከስምምነቱ እንድትወጣ ካደረጓቸው ምክንያቶች መካከል አንዱና ዋነኛው የወዳጃቸው እስራኤል ግፊት እንደሆነ እየተገለጸ ነው፡፡ ሰውየው የአሜሪካ ጠንካራ አጋርና ወዳጅ የሆነችውን እስራኤልን ለማጥፋት እቅድ አላት የምትባለው ኢራን የኑክሌር መሳሪያ ታጥቃ ማየት አይፈልጉም፡፡ የልጃቸው ኢቫንካ ትራምፕ ባለቤት የሆኑት አይሁዳዊው ጃሬድ ኩሽነር የፕሬዚዳንቱ ከፍተኛ አማካሪ መሆን ደግሞ ትርጉሙ ብዙ ነው የሚሉ አካላትም አሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ እስራኤል የትራምፕን ውሳኔ በደስታ ተቀብላዋለች፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከምዕራብ ኢየሩሳሌም ሆነው በሰጡት መግለጫ፣ አሜሪካ አደገኛ ከሆነው ስምምነት መውጣቷን ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፉት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ስምምነቱ ኢራንን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት ስለሚያደርጋት እስራኤል ከመጀመሪያው ጀምሮ ስምምነቱን ስትቃወም ነበር፤ የፕሬዚዳንት ትራምፕ ውሳኔም ትክክለኛ ነው›› ብለዋል፡፡
ሳዑዲ አረቢያ፣ ባሕሬንና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችም ለትራምፕ ውሳኔ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡ የኢራን የቀጣናው ዋነኛ ባላንጣ የሆነችው ሳዑዲ አረቢያ የፕሬዚዳንቱን ከስምምነቱ መውጣትና በኢራን ላይ ማዕቀቦችም እንዲጣሉባት ያላቸውን ሃሳብ እንደምትደግፍ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ በኩል ይፋ አድርጋለች፡፡
የኢራን ኑክሌር ስምምነት እንዲፈረም ያደረጉት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ጆን ኬሪ፣ የትራምፕ ውሳኔ የአሜሪካንና የእስራኤልን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል፣ ከአውሮፓ አጋሮቻቸው ጋር የሚያቃቅር እንዲሁም ኢራንን ከእኩይ ተግባሮቿ ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፍ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ይሁን እንጂ ዶናልድ ትራምፕ ይህ ሁሉ ውግዘትና ተቃውሞ እየደረሰባቸው ከስምምነቱ በመውጣት ብቻ አላቆሙም፡፡ አሜሪካ በኢራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን እንደምትጥልና ኢራንን የሚያግዙ አገራትም የማዕቀብ ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
(የመረጃው ምንጮች ፡ አልጀዚራ እና ቢቢሲ)

አንተነህ ቸሬ

Published in ዓለም አቀፍ

ማንም ሰው ስለሰላም ሲያስብ የየራሱ ምልከታ ይኖረዋል፡፡ ሰላምን በአግባቡ ሊበይነው የሚችለውም ከጥልቅ አመለካከትና ጠቀሜታውን ከመገንዘብ አኳያ ሊሆን እንደሚችል መረዳት አያዳግትም፡፡ የሰላም ዋጋ በገንዘብ የሚተመን ባይሆንም ሁሉም ሰው በቀላሉ ሊገዛው ግን ይችላል፡፡
ሰላም በእጃችን ሲኖር እንደ አልባሌ ነገር እንቆጥረዋለን፡፡ ሲያመልጠን ግን ዋጋውን መገመት ያስቸግረናል፡፡ መልሶ የማግኛው መንገድና ዋጋው የማይደረስበት ይሆናል፡፡ ይህ እንዳይሆን ግን ከመጀመሪያው እንዳያመልጠን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በእጃችን ያለው ሰላም ዋጋው አልባሌ የሚሆንብን ትዕግሥታችንንና መቻቻላችንን መሰረት በማድረግ ችግሮቻችንን በመወያየት መፍታት ሳንችል ስንቀር ነው፡፡ አስተሳሰባችን የበሰለ ሲሆን የምንወያይበት ታላቁ ርዕሰ ጉዳያችን አገራችንን ያስቀደመ ስለሚሆን የሰላማችን ጉዳይ ስጋት ያለበት አይሆንም፡፡
ይሁን እንጂ በሌሎች ሰላማቸውን ባጡ አገሮች የምናየው ሁኔታ እኛ ላይ ባለመከሰቱና ለጊዜው በሰላም መኖር መቻላችን ብቻ የሰላም እጦት በእኛ አይደርስም ብሎ ማሰብ እጅግ ሞኝነት ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት በሰላም እጦት ምክንያት ችግር ውስጥ ከሚገኙ ሀገራት መካከል ሶሪያ፣ የመን፣ ኢራቅና ደቡብ ሱዳን ቀዳሚ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል ሶሪያና የመን በእርስ በርስ ጦርነት መነሻ ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል፡፡ የዓለም የስልጣኔ ማማ ላይ ደርሳ የነበረችው ኢራቅ በአሸባሪ ቡድኖች ተልዕኮ ታላላቅ የስልጣኔ አሻራዎቿን አጥታ ህዝቧ ለሞትና ለስደት ተዳርጓል፡፡
የአንድ አገር የሰላም እጦት ሞት፣ አካላዊ ጥቃት፣ መፈናቀል፣ ስደት፣ ወረርሽኝ፣ በሽታና ርሃብ ያስከትላል፡፡ ሰላም አጥተዋል የምንላቸው አገራት ለእነዚህ ችግሮች ተዳርገዋል፡፡ በሰላም መደፍረስ ምክንያት በሚከሰቱ ችግሮች ተጠቂ ከሆኑት መካከል አብዛኞቹ ህጻናትና ሴቶች መሆናቸው ሲታሰብ ለሰላም መኖር ውድ ዋጋ ሊከፈል እንደሚገባ የሚያስገነዝብ ነው፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን በተለይም አሁን ከምንተዳደርበት ሥርዓት በፊት የነበሩ የጦርነት፣የርሃብ፣የስደትና የዴሞክራሲ እጦት ተሞክሮዎቻችን መሰረት በማድረግ በአሁኑ ወቅት ያለንን ካልመዘንንና ካላከበርን ሌሎች አገሮች የደረሰባቸው ዕጣ ፋንታ የእኛ ድርሻ እንደሚሆን መረዳት ሊሳነን አይገባም፡፡
ለእኛ ይጠቅማሉ በሚል በምሳሌነት ያነሳናቸው አገራት በእርስ በርስ ጦርነት ዘመናት የተገነቡ የቀደሙት የስልጣኔ አሻራዎቻቸው በጥቂት ሰዓታት የወደሙት፣ ሰማይ ጠቀስ ህንጻዎቻቸው ወደ ፍርስራሽነት የተቀየሩት፣ በሰላም ወጥቶ መግባት የናፈቃቸውና ሕይወታቸው አደጋ ላይ መውደቁ፤ ዜጎቻቸው ሰላማዊ ህይወት ፍለጋ ድንበርና ባህር ለማቋረጥ መሰቃየታቸው ለሰላም የሰጡት ዋጋ አነስተኛ በመሆኑ ነው፡፡
የእነዚህን ሀገራት የጦርነትና የውድመት ችግሮች አነሳን እንጂ የራሳችንን ሰላም ማጣትና የሚያደርስብንን ጉዳት በወጉ ማወቅ ያልቻልን በርካቶች እንደሆንን አይካድም፡፡
ከ27 አመታት በፊት ሰላም ባለመኖሩ መላውን የአገሪቱ ዜጎች ለጦርነት በመማገድ የሚያለሙ ሃይሎች የሕይወትና የአካል መስዋዕትነት እንዲከፍሉ፣ ለልማት ይውል የነበረ ሀብት ለመሳሪያ መግዣ ውሎ ዜጎች ከድህነት ወለል በታች እንድንሆን አድርጓል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ መላው አገራዊ ጉዳት ያንገበገባቸው የአገሪቱ ውድ ልጆች አስከፊውን ስርዓት ለመታገል ቆርጠው በመነሳታቸውና በመታገላቸው ታላቅ መስዋዕትነት ከፍለው ውጤታማ በመሆን ግንቦት 20 ቀን ለድል በቅተዋል፡፡
አገሪቱ ያጣችውን ሰላም ለማስፈን ብዙ ተጋድሎ ተደርጎ ፊታችንን ወደ ልማት በማዞር የተመዘገቡት የልማት ድሎችም ውጤት የተገኘባቸው ሌላኛው የተጋድሎ ታሪካችን ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ አገራችን በአፍሪቃ ቀንድ መገኘቷ በሰላማችን ላይ የሚያሣድረው ተጽእኖ ቀላል ባይሆንም ለሰላም መደፍረስ መንስኤ የሆኑ ውስጣዊ ችግሮችን በመፍታት ላይ በትኩረት በመሰራቱና ተገቢውን የውጭ ፖሊሲና ስትራቴጂ በመከተላችን ለአፍሪቃ የሰላም ዘብ መሆን ችለናል፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ባለፉት 27 ዓመታት በተፈጠረው አስተማማኝ ሰላም ያገኘነውን የልማትና የዴሞክራሲ ድሎች በሚገባ እናውቃለን። ከሰላም ያገኘነው ጥቅም በምንም መስፈርት የሚለካ ሊሆን አይችልም፡፡
በአንድ በኩል በአገሪቱ የሚገኙ የሰላም ቀበኞች፤ በሌላ በኩል ደግሞ በውጭ የሚገኙ ፅንፈኛ ተቃዋሚዎች ጎራ በመለየት ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ እንዳይተማመኑ አፍራሽ ሴራ በመሸረብ አገሪቱ እንድትበታተን ጥረት ማድረጋቸው ይታወሳል።
በአጥፊ ተግባር ላይ የተሰማሩት የውስጥና የውጭ ጠላቶች በተቀነባበረ አፍራሽ ዘመቻ በአገር ግንባታ፣ ልማትና ድህነትን በማጥፋት ሥራ የተጠመደን መንግስትና ሕዝብ በማቃቃር፣ ብሄርን ከብሄር በማጋጨት፣ የነገ ተስፋን የሰነቁ ወጣቶች በትምህርት ገበታቸው ላይ ተረጋግተው እንዳይሰማሩ በመቀስቅሰ ጥፋትን እያዘጋጁ ሲያበጣብጡ ቆይተዋል፡፡
ቀደም ሲል በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የተከሰቱ ቅራኔዎችም የዚሁ መጥፎ ተግባር መንስኤ በመሆናቸው በአፍራሽ ስብከት የተጠመደው የሕብረተሰብ ክፍል በመልካም የዕድገትና የልማት ጎዳና እየተራመደች የምትገኘውን አገር ነባራዊ ሁኔታ በመዘንጋት ትርምስ ውስጥ እንድትወድቅ አስተዋፅዎ የሚያደርግ የእኩይ ተግባር ሰለባ ሆኖ ታይቷል፡፡
በእውነተኛ ሕዝባዊ ትግል በተከፈለው መስዋዕትነትና በበርካታ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ በማለፍ የተገኘው ሰላም፣ የተጀመረው የዕድገት ጉዞና የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት ከንቱ እንዲቀር ብሎም አገሪቱ አደጋ ላይ እንድትወድቅ የሚጋብዝ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ጥረት የሚያደርጉ ሃይሎች አሁንም እንዳሉ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ልብ ሊለው ይገባል፡፡
በየትኛውም ጊዜ አገሪቱን ለማጥፋትና ሕብረተሰቡን ለማበጣበጥ ጥረቶች ይደረጉ እንጂ ሰላም ወዳዱ አብዛኛው ሕብረተሰብ የከፋፋዮችን ሃሳብ ሲቀበልና በተግባር ሲያውል አልታየም፡፡ በተለይም ወጣቱ ትውልድ በጥቂቱም ቢሆን በመረጃ ክፍተት ለተንኮለኞች ስውር ደባ ቢጋለጥም በአገሪቱ ያለውን እውነታ በመረዳት ስህተትን በማረም ወደሚጠቅመው የሰላምና የልማት አቅጣጫ በማዘንበል የሴረኞችን ዓላማ እያከሸፈ ይገኛል፡፡
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓቢይ አህመድ እንደተናገሩት ምንም እንኳ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ቢያድግም አብሮት የመጣው ችግር ኪራይ ሰብሳቢነት ሆኗል፡፡ የልማታዊ ፖለቲካ ኢኮኖሚ በኪራይ ሰብሳቢነት ላይ የበላይነቱን እስከሚያረጋግጥ ድረስም ኢሕአዴግ ሆነ መንግስት የጀመረውን ጥረት ከፍፃሜ ሊያደርስ የሚችለው መላው ህብረተሰብ በየትኛውም ቦታ ለመልካም አስተዳደር መስፈን የበኩሉን አስተዋፅዎ ማድረግ ሲገባው እንደሆነ ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰቱ ሁከቶችና ግጭቶች የሰው ሕይወት መጥፋቱ፣ ንብረት መውደሙና ዜጎች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸው ትልቅ ጠባሳ ጥሎ ያለፈ ክስተት ነው። ሁከቱን በቁጥጥር ስር ማዋል እንዲቻል መንግስት ባለፈው አመት በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰላሙን አጥቶ የነበረው የህብረተሰብ ክፍል አንፃራዊ ሰላም አግኝቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ የሰላሙ መመለስ ያስደሰተው ህብረተሰብ ለአዋጁ ተግባራዊነት ያደረገው አስተዋፅዎ የላቀ ቢሆንም፤ ከአዋጁ መነሳት በኋላ ሁከቱ በማገርሸቱ መንግስት ዳግም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ተገዷል፡፡ መንግስት ለችግሩ ከፍተኛውን ሃላፊነት በመውሰድ ለሰላምና መረጋጋት የመፍትሄ አካል ለመሆን ሲባል በግልፅ ተናግሯል፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የኃላፊነት ቦታን እስከመልቀቅ የደረሰ ዕርምጃ ወስደዋል፡፡
ወቅታዊውን ያለመረጋጋትም እልባት ለመስጠት በአሁኑ ወቅት እየተተገበረ ያለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአመዛኙ በየቦታው ለታየው ሁከት፣ ረብሻና ስርዓት አልበኝነትን በመግታት፤ ሀገራችንና ህዝቦቿ የጀመሩትን የልማት ጉዞ የሚያስቀጥል ሆኗል፡፡
መረጋጋትና ሰላም በሌለበት የሚፈለገውን የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳካት አይቻልም። ሰላም ከሌለ የብጥብጥ ቀስቃሾች ያለሙትን ያሳካሉ። የልማት ኃይል የሆነውን ዜጋ በማሰባሰብ ለጥፋት ድርጊታቸው ዓላማ ያውሉታል፡፡ የሰላምን ጥቅም ያልተረዳ ዜጋ ሚዛናዊነት ጎድሎት በጊዜያዊ ስሜት በመገፋፋት አገሩን የሚጎዳ ተግባር ይፈፅማል፡፡ የሰላም እጦት የዜጎችን ክቡርና የማይተካ ህይወት ይነጥቃል፡፡ ጥፋቱ ግን ካለ ልዩነት ሳያደርግ ሁሉንም የሚጎዳ እንጂ አንዱን ተጎጂ አንዱን ተጠቃሚ የሚያደርግ አይሆንም፡፡ የሰላም እጦት መላ የአገሪቱን ሀብት ያወድማል።
በአፍላ ስሜት ላይ ያሉት ሁሉ ሰላም በእጃቸው እያለ ያቀለሉት ወይም ያላከበሩት ከእጃቸው ከወጣ በኋላ ያንን ያመለጣቸውን ጊዜ ወደ ኋላ መለስ ብለው ሲያጤኑት ለቁጭት እንደዳረጋቸው ከወዲሁ በመረዳት ሰላም የሁሉም መሰረት መሆኑን ታውቆ ከሰላም ሁለንተናዊ ጥቅምን ለማግኘት ሁሉም ህዝብ ጥረት ማድረግ ይገባዋል፡፡

መዝገቡ ሃይሌ

Published in አጀንዳ

ከ27 ዓመታት በፊት ሲያስተዳድረን በነበረው የመንግሥት ሥርዓት ውስጥ የወጣቶች አደረጃጀትና እንቅስቃሴዎች ሁሉ በወቅቱ ከነበረው የፖለቲካ አመለካከትና ፍላጐት ጋር በመጣመራቸው ወጣቶች በውትድርና እንዲያገለግሉና በጦርነት እንዲያልቁ የተፈረደባቸው ሆነው እስከመታየት መድረሳቸው ይታወሳል፡፡
በዚህ ፈታኝ ወቅት ሥርዓቱን በመቃወም አያሌ ወጣቶች ለሕዝቦች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ሲሉ የሕይወት መስዋዕትነት እስከመክፈል ደርሰዋል፡፡ ይህ ረጅም የትግል ጉዟቸውና መስዋዕትነታቸው አገሪቱ አሁን ለምትገኝበት የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንድትበቃ አስችሏታል፡፡
ኢትዮጵያውያን ወጣቶች አገራቸው ከጦርነት ተላቅቃ የተረጋጋ ኑሮ ከጀመሩ ወዲህ በተፈጠረላቸው ሰላምና ተደራጅቶ የመስራት ምቹ ሁኔታ በተለያዩ የስራ መስኮች በመሰማራት ከአነስተኛ ደረጃ ወደ ከፍተኛ ደረጃ መሸጋገራቸው እንደ አብነት ይጠቀሳል፡፡
ዜጎች አገሪቱን አሁን የደረሰችበት ደረጃ ለማድረስ በአካልም በገንዘብም በከፈሉት መስዋዕትነት በዓለም አቀፍ ደረጃ በፈጣን ዕድገት ምሳሌ መሆናችን አስከፊ የነበረው ገፅታችን መለወጡን የምናይበት በመሆኑ ልባችን በደስታ ይሞላል፡፡ ይህ ሂደታችን በቀጣይ ከዚህ በበለጠ ከፍ የምንልበትን ተግባር የምናከናውንበት እንጂ ባገኘነው ድል ተኩራርተን እጆቻችንን አጣጥፈን እንድንቀመጥ አይጋብዘንም፡፡
መጪው ጊዜ የአገራችንን ስም በበለጠ መልካምነትና በዕድገት የምትጠራበት እንዲሆን ዛሬ የምናከናውነው በጎ ተግባር መሰረት ስለሚሆን ለነገ የላቀ ዕድገታችን እያንዳንዷን የዛሬ ተግባራችን በእጅጉ አስፈላጊ ለሆነው ሰላም በንቃት በመቆም ማስመስከር ይኖርብናል፡፡
መላው ኢትዮጵያውያን መቼውንም ቢሆን ማንኛውም ተግባር ሲከናወን ሁሉም ጉዞ አልጋ በአልጋ እንደማይሆን በመረዳት፤ችግሮች ሲያጋጥሙ በውይይት በመፍታት እስካሁን የተገኘውን ድል ወደተሻለ ደረጃ ማሳደግ ተገቢ ተግባር መሆኑን መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡
ያለፉት 27 ዓመታት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጉዞዎቻችን የመስዋዕትነት ውጤቶች ናቸው፡፡ እነዚህን ድሎቻችን የበለጠ ፍሬ እንዲያፈሩ ለማድረግም እንደ ከዚህ ቀደሙ ተግባራችን ችግሮቻችንን በእርጋታና በትዕግስት ፈትሸን መፍትሄ እያፈላለግን ልማታችንንና የዕድገት ጉዞአችንን ሳናስተጓጉል መራመድ ይኖርብናል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት ያጋጠሙን ያለመረጋጋት ክስተቶች ለአገር በማሰብና በተረጋጋ ሁኔታ ምልከታ የተደረገባቸው ቢሆኑ ኖሮ ከየክልሉ ለተፈናቀሉ፣ሕይወታቸው ለጠፋ፣አካላቸው ለጎደለና ንብረታቸው ለወደመ ወገኖቻችን ጉዳት መንስዔ ባልሆኑ ነበር፡፡
በወቅቱ ተከስቶ ከነበረው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ መንግስት ለወሰዳቸው ዕርምጃዎች ተጠያቂ ነኝ በማለትና ለመፍትሄው መገኘት ቀዳሚ በመሆን በአፍሪካ በዓርአያነቱ የሚጠቀስ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር መደረጉ አገሪቱ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደደረሰች ማሳያ ሆኗል፡፡
ሥልጣን ለመያዝ የሕይወት መስዋእትነት እየተከፈለና የስልጣን እድሜን ለማራዘም ሲባል ህገ-መንግስት በሚቀየርበት አፍሪካ ምድር ፍጹም ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ማድረግ መቻል ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለአለም ተምሳሌት የሚያደርገን ነው፡፡ ይህም አገሪቱ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሰጠችውን ትኩረት እንዲሁም የአመራሩን ቁርጠኝነት አመላክቷል፡፡
ይህ ሁሉ የሆነው ግን ለሰላም፣ ለዴሞክራሲ ግንባታና ለነፃነት ሲባል በተከፈለ መስዋዕትነት እንጂ ከማንም በተገኘ በችሮታ አይደለም፡፡ ዛሬም የአገሪቱ ዜጎች የሚፈልጉትን ዕድገትና ብልፅግና ማግኘት የሚችሉት ተግቶ በመስራት እንጂ ለአፍራሽ ተልዕኮ እንደሚንቀሳቀሱት በሁከትና በብጥብጥ ከሚገኝ ዕልቂት አይደለም፡፡
ዛሬ ለጦርነት የሚታጭ ዘማች የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ አይደለንም፡፡ ዘመቻችን ሰርቶ ማግኘትና ሕይወትን የመለወጥ ተግባር ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የህይወትም የአካልም መስዋዕትነት የከፈሉልን አባቶቻችን፣እናቶቻችን፣ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያስረከቡንን ሰላም በመጠበቅ በአንድነት መንፈስ የየበኩላችንን ድርሻ ለአገራችን ማበርከት ይጠበቅብናል፡፡

 

Published in ርዕሰ አንቀፅ

 

 «ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ» እንዲሉ ዶክተር አቅናው ዋቅጋሪ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሥራውን በጀመረ በዓመቱ ዩኒቨርሲቲውን በመቀላቀሉ የመማር ማስተማሩን ሂደትና ለውጥ ከመሰረቱ ያውቀዋል፡፡
ወለጋ ዩኒቨርሲቲ በ1999ዓ.ም የመማር ማስተማር ሥራውን እንደጀመረ ተማሪዎች የግቢው ኮብል ስቶን ንጣፍ አልተመቸንም፣የተለያየ ምግብ አይቀርብልንም፣ኢንተርኔቱ ይቆራረጣል፣መዝናኛው ያንሳል ወዘተ... እያሉ የሚያነሱዋቸው ጥያቄዎች የቅንጦት ነበሩ። በዩኒቨርሲቲው አንድ ቤተመጽሐፍት፣አንድ የመመገቢያ ክፍል፣ውስን የመማሪያ ክፍሎችና የተማሪ ማደሪያዎች ብቻ ነበሩ አገልግሎት የሚሰጡት፡፡መምህራን ቢሮ አልነበራቸውም፤ አንድ ህንፃ ተገንብቶ ሲያልቅ ወንበራቸውን እያጓጓዙ ወደሌላኛው በመሄድ ነበር የመምህርነት ሥራቸውን የሚወጡት፡፡
የተማሪዎች መዝናኛ የሚታሰብ አልነበረም፡፡ የግቢው ጭቃ እግርኳስና የተለያዩ ስፖርታዊ ጨዋታዎችን ለመጫወት ቀርቶ እንደልብ ለመራመድም የሚያስችል አልነበረም፡፡የተማሪዎች መመገቢያ ባለመደራጀቱ ምግብ በግዥ ከውጭ ነበር የሚቀርበው፡፡ማጣቀሻ መጽሐፍት፣ቤተሙከራ የመሳሰሉት የትምህርት ግብአቶች አልተሟሉም ነበር፡፡
በዩኒቨርሲቲው የእንስሳት ህክምና ክፍል ለአምስት ዓመታት ትምህርቱን የተከታተለው ዶክተር ዋቅጋሪ ከ2005ዓ.ም ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው በተማረው ትምህርት በእንስሳት ህክምና ትምህርት ክፍል ውስጥ በመምህርነት በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡በ11ዓመት ቆይታው በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ለውጥ ማየቱንና እርሱም የለውጡ አካል መሆኑ እንደሚያስደስተው ይገልፃል፡፡ዩኒቨርሲቲው በተሟላ አደረጃጀት እስከ ሦስተኛ ዲግሪ የማስተማር አቅም ገንብቶ ከስመጥር ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ሆኖ ለመገኘት ሌት ተቀን በመስራት ላይ እንደሆነ ተናግሯል፡፡
የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኤባ ሚጀና ዩኒቨርሲቲው ከ11ዓመት በፊት በውስን የትምህርት ዓይነቶች 851ተማሪዎችን ተቀብሎ በመጀመሪያ ዲግሪ የመማር ማስተማር ሥራውን ሲጀምር ቤተሙከራና በቂ የሰው ኃይል እንዳል ነበረው፤139 መምህራንና154 ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ብቻ በመያዝ ግንባታዎችን እያከናወነና የትምህርት ክፍሎችን እያስፋፋ ለውጥ ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ እንደገለጹት በአሁኑ ጊዜ በመደበኛ፣በማታ የትምህርት ክፍለጊዜና በርቀት 34ሺ791ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ሲሆን፣በመጀመሪያ ዲግሪ በ101፣በሁለተኛዲግሪ በ79፣በሦስተኛ ዲግሪ በ8 የትምህርት ዓይነቶች በ1ሺ300መምህራን የመማር ማስተማር ሥራውን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ መምህራንን ለማብቃትም ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡በአሁኑ ጊዜም 442 መምህራን በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ በመማር ላይ ይገኛሉ፡፡
ዩኒቨርሲቲው ኢትዮጵያ በ2017ዓ.ም መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች አንዷ ለመሆን የሚያስችላትን እቅድ ነድፋ የምታደረገውን እንቅስቃሴ መሠረት ያደረገ የ17 ዓመት ዕቅድ መንደፉንና ዕቅዱንም ለማሳካት የሚያስችሉ ሥራዎችን ከወዲሁ በማከናወን ላይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
እንደ ዶክተር ኤባ ማብራሪያ ዩኒቨርስቲው በትምህርት ጥራት ላይ ትኩረት አድርጎ ተማሪ ተኮር የሥርዓተ ትምህርት ክለሳ ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ተጠናቅቋል፤ተማሪው ዕውቀት ያለው ሆኖ እንዲወጣም በትምህርት ቆይታው ለመመረቅ ብቻ ሳይሆን የሚሰራው ምርምር ችግር ፈቺ ይሆናል፡፡
ኢንዱስትሪው ወይም ገበያው የሚፈልገውን የሰው ኃይል ማፍራት የሥርዓተ ትምህርት ክለሳው አካል ሲሆን፣ይህንን ለመተግበር በዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ አካላት የተውጣጡ አባላት ያለው ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ ነው፡፡ዩኒቨርሰቲው እቅዱን ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር መክሮበት በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀቱን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
የቤተሙከራ ክፍሉን በተሻለ ለማደራጀት ዓለምአቀፍ የቤተሙከራ ቁሳቁስ ግዥ መፈፀሙን የጠቆሙት ዶክተር ኤባ በሀገር ውስጥ መሟላት ያለባቸው ግብዓቶች በአቅርቦት እጥረትና በተለያየ ምክንያት በሚፈለገው ፍጥነት ለማሳካት ተግዳሮት እንዳጋጠመ ገልፀዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው በነበረኝ ቆይታ ካነጋገርኳቸው ተማሪዎች የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል የሦስተኛ ዓመት ተማሪ የሆነችው ተማሪ ብርሃን ነገሠ በሦስት ዓመት የትምህርት ቆይታዋ በፈተና ወቅት አንዳንድ የማጣቀሻ መጽሐፍት ለማግኘት ከሚያጋጥመው ችግር በስተቀር የጎላ ነገር እንዳላጋጠማት ገልፃለች፡፡
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አማካኝነት በቀረበ የትምህርት ዕድል የህክምና ትምህርት በመከታተል ላይ የሚገኘው ተማሪ ሰይፈዲን ሙዘይን ዩኒቨርሲቲው ለትምህርቱ የሚያስፈልገው ኮምፒዩተር አሟልቶለት ትምህርቱን በመከታተል ላይ መሆኑንና በአንድ ዓመት የትምህርት ቆይታው ያጋጠመው ችግር እንደሌለ ተናግሯል፡፡
ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ትውልድ ውስጥ ከሚገኙት የትምህርት ተቋማት አንዱ ሲሆን፣በአሥር ዓመት ውስጥ በመማር ማስተማር ሥራው ያስመዘገባቸው ውጤቶች በተለያየ ጊዜ ለዋንጫ ሽልማት እንዲበቃ አስችለውታል፡፡

ዜና ሐተታ
ለምለም መንግሥቱ

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።