Items filtered by date: Saturday, 12 May 2018

ከሳምንት በፊት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሃያ ሁለተኛ ሳምንት አዲስ አባባ ስቴድየም ላይ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ከመከላከያ ባደረጉት ጨዋታ አልቢትር እያሱ ፈንቴ ላይ የደረሰውን ድብደባ ተከትሎ የስፖርታዊ ጨዋነት ጉዳይ ትልቅ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል። የፌደራል ዳኛ ኢያሱ ፈንቴን የወልዋሎ ተጫዋቾች እና የቡድን መሪው አቶ ማሩ ገብረፃድቅ በዳኛው ላይ ባደረሱት ድብደባ በኋላ ጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት አግኝቶ በዓለም አቀፍ ሚድያዎችም ጭምር ሲዘገብ ቆይቷል። የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ልዑልሰገድ በጋሻው የእግርኳሱ የበላይ አካል ፊፋ እና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በዳኛው ላይ ድብደባ የፈፀሙት አካላት ላይ የሚወሰደውን የዲሲፒሊን ውሳኔ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዲያሳውቀው ደብዳቤ መላኩን ተናግረዋል። የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ ግን ስለ ደብዳቤው መላክ የሚያውቁት ጉዳይ እንደሌለ ተናግረዋል።

ከሚያዝያ 25 - ግንቦት 20/2010 ድረስ የእግር ኳስ ውድድሮችን ላለመምራት የወሰነው የዳኞች እና ታዛቢዎች ማህበር ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር አስር ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጦ ከትናንት በስቲያ ማምሻውን በጁፒተር ሆቴል ተደራድሯል። በዚህም መሰረት በውይይቱ ውድድሩን ለመቀጠል ከአስር ድምፅ በዘጠኙ ይሁንታ ከስምምነት ላይ ደርሷል፡፡የፕሮግራም ሽግሽግ ተደርጎም ተስተካካይ ጨዋታዎች በወጣላቸው ፕሮግራም ይቀጥላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግም ከሰኞ ጀምሮ ይካሄዳሉ።
በውይይቱ ዳኞች ቀደም ብሎ ያነሱትን ጥያቄ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በአቶ ጁነይዲ ባሻ በኩል አንድ በአንድ ምላሽ ለመስጠት ሞክሯል። በ2010ዓ.ም የውድድር ዘመን ሜዳ ላይ የተጎዱ ዳኞች ተገቢው ካሳ እንዲያገኙ የሚለው የሙያ ማህበሩ ቀዳሚ ጥያቄና ከአስሩ አቋም አንደኛው ነው። በዚህም መሰረት ፌዴሬሽኑ የካሳ ጉዳይ የጉዳቱ መጠን ተጠቅሶ እና ማስረጃዎች ታይተው በዲሲፒሊን ኮሚቴ ተጣርቶ ተፈፃሚ እንደሚሆን ገልጿል። ዳኞች ውድድሩን ከመጀመራቸው በፊት በውድድር ደንቡ መሰረት ኢንሹራንስ ወይንም ዋስትና መጠየቃቸው ይታወቃል። ይህም ጥያቄ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከ2011 ጀምሮ የዳኞች መድን ዋስትና እንዲኖር ይደረጋል የሚል ምላሽ ተሰጥቶታል። ይህ ካልተሟላም የቀጣዩ ዓመት ውድድር እንዳይጀመር ይደረጋል። ለ ሁለት ወራት ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም ለሃያ ዳኞች እና ታዛቢዎች ውድድሩ እስኪጠናቀቅ ድረስ የመድን ዋስትና እንደሚገባ ፌዴሬሽኑ አሳውቋል።
ወልዲያ ከተማ ከፋሲል ከተማ ባደረጉት ጨዋታ ጉዳት የደረሰበት ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ በአገር ውስጥም ሆነ ውጪ ተገቢውን ህክምና እንዲደረግለት የተነሳው ጥያቄ ሌላኛው ነው። የሙስጠፋ መኪ ጉዳይ በዲሲፕሊን ኮሚቴ ቅጣቱ ውሳኔ መሰረት አስፈላጊውን የህክምና ወጪ ብቻ ሳይሆን ካሳም ወልዲያ ከተማ እግር ኳስ ክለብ እንደሚከፍል የተነገረ ሲሆን በተጨማሪም ፌዴሬሽኑ መቶ ሺ ብር ለመስጠት ወስኗል።
ከክልል የፀጥታ አካላት ጋር በመግባባት የዳኞች ጥበቃ እንዲደረግ ለተጠየቀው ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የፀጥታ አካላት ፣ ወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ተወካዮች እንዲሁም የዳኞች ማህበር የሚገኙበት ምክክር ለማድረግ መወሰኑንም ፌዴሬሽኑ አሳውቋል።
በወንዶች እና በሴቶች ፕርሚየር ሊግን ለመዳኘት የጉዞ ወቅት አውሮፕላን የሚደርስበት ቦታ ሁሉ ትራንስፓርት እንዲመቻች የቀረበው ጥያቄ የአየር ትራንስፖርት ለማመቻቸት እስከ ዘንድሮው የወንዶች ውድድር ማብቂያ ድረስ የሚሆን ገንዘብ ክለቦች እንዲሸፍኑ ይደረጋል። ይህ የማይቻል ከሆነ ግን ለ2011 የውድድር ዘመን የሚጀመር ይሆናል።
የአልቢትር እያሱ ፈንቴን ጉዳይ ጨምሮ ፓሊስ ያወቃቸው የስርዓት አልበኝነትና የዳኞች የመብት ጥሰቶች ተገቢውን የህግ ፍርድ እንዲያገኙም ጥያቄ መቅረቡ ይታወቃል። የአልቢትር እያሱ ፈንቴ የመብት ጥሰት ጉዳይ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፍርድ ቤት ጉዳዩ እንደተያዘ ተገልጿል። ተበዳዩም ቀርቦ ቃሉን የሰጠ ሲሆን የፌዴሬሽኑ የህግ ክፍል ማንኛውንም ድጋፍና ክትትል በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተብራርቷል። ፌዴሬሽኑ ለዳኞች እና ለታዛቢዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያመቻች ለተነሳው ጥያቄም የአቅም ግንባታ ስልጠና እንዲሰጥ መወሰኑ ተገልጿል።
ማህበሩ ያለ አግባብ ለጠቅላላ ጉባኤ ያወጣው ወጪ በፌዴሬሽኑ በህጋዊ ደረሰኝ አማካኝነት እንዲመለስ የተነሳው ጥያቄ ግን በፌዴሬሽኑ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴዎቹ አሰራር በግልፅ እንዲጠየቅ በተጠየቀው መሰረትም የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ስራውን እንዲያቆም መታገዱ ታውቋል። ተገቢው የህግ ከለላ በሌለባቸው ስታዲየሞች ውድድር እንዳይካሄድ ለተነሳው ጥያቄም ከ2011 የውድድር ዓመት ጀምሮ ማንኛውንም አጥር የሌለው ሜዳ ውድድር እንዳያካሂድ ይደረጋል የሚል ምላሽ ተሰጥቷል።
በአጠቃላይ ዳኞችና ታዛቢዎች ያነሱት ጥያቄ ፌዴሬሽኑ ከሞላ ጎደል በቃል ደረጃ መልሶታል ተብሎ ይታሰባል። ዳኞች በወሰዱት አቋም ከዚህ በኋላም ራሳቸውን ለማስከበር ትልቅ እርምጃ መሆኑን በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል። ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ ምላሾች ወደ ተግባር ሲወርዱ በምን መልኩ ሊከወኑ እንደሚችሉ ግልፅ አይደሉም። ይሁን እንጂ ፌዴሬሽኑ በተገቢው መልኩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ ከቻለ በመጠኑም ቢሆን የዳኞቹን ስጋት ሊቀንስ እንደሚችል ይታመናል።
ዳኞች ለደህንነት ዋስትና ያላቸው ስቴድየሞች ውስጥ ጨዋታዎችን እንዲመሩ ፌዴሬሽኑ የትኛውም ክልል የሚገኙ ክለቦች ሜዳዎቻቸውን እንዲያሳጥሩ አደርጋለሁ ብሎ የሰጠው ምላሽ ለብዙዎች ያልተዋጠ ሲሆን በአግባቡ ተጤኗል ለማለትም አይቻልም። ክለቦች አቅሙ ኖሯቸው ይህን ማድረግ ቢችሉ እንኳን ዳኞች በዚህ ብቻ ደህንነታቸው ይረጋገጣል ተብሎ አይታሰብም። ምክንያቱም ዳኞች ድብደባ እየደረሰባቸው ያለው ከደጋፊዎች ብቻ ሳይሆን በቡድን መሪዎች፤ አሰልጣኞችና ተጫዋቾች ጭምር መሆኑን በአልቢትር እያሱ ፈንቴ ላይ የተከሰተውን ማንሳት በቂ ነው። ሜዳን ማሳጠር ደጋፊዎች ወደ ሜዳ ገብተው ዳኞች ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ በተወሰነ ደረጃ የሚጠቅም መሆኑ ቢታመንም በዋናዎቹ የሜዳ ላይ ተዋናዮች ቡድን መሪ፤ አሰልጣኝና ተጫዋች ሊሰነዘር የሚችል ጥቃትን ጭምር ማቆም የሚችለው አጥር ሳይሆን ጠንካራ ህግ ነው። ለዚህም ከፌዴሬሽኑ በተጨማሪ ክለቦች የራሳቸውን ጠንካራ ህግ ማርቀቅ ይኖርባቸዋል። መቀሌ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ለዚህ ምሳሌ ሊሆን ይችላል። ይህ ክለብ ከዳኛ ጋር እንኳን ለፀብ መጋበዝና ቡጢ እስከ መሰንዘር ግብ ግብ ለመፍጠር የሞከረ ተጫዋች ደመወዙን ይቀጣል።
ዳኞች ለተጫዋቾች ቀይ ካርድ ሲያሳዩ ቅጣቱ እንደሚነሳላቸው ተጫዋቾች በሙሉ ልብ ሜዳ ላይ እንደሚናገሩ በውይይቱ ወቅት ዳኞች ያነሱት ጉዳይ የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ነው። ይህን የሚያደርገው የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ነው። ፌዴሬሽኑ ለጊዜው ይህን ኮሚቴ ማገዱን ቢያሳውቅም ማገድ ብቻ በቂ አይደለም። ይህን የሚያደርገው አንድ ግለሰብ እንደሆነ ተጠቁሟል። ይህን አድርጓል የተባለው ግለሰብ ከኮሚቴው ማስወጣት ብቻም ሳይሆን ጉዳዩ ተጣርቶ እውነት ከሆነ በህግ እስከ መጠየቅ መድረስ አለበት።

 

ሩሲያ- የአንድ ወር የዓለም ቀልብ ማረፊያ

 

ሃያ አንደኛው የዓለም ዋንጫ በሩሲያ አስተናጋጅነት ሊጀመር ከወር ያልበለጠ ጊዜ ቀርቶታል። ይህን ቁጥር አንድ ተወዳጅ የዓለማችን ውድድር የተሳካ ለማድረግ አዘጋጇ ሩሲያ ሽርጉዷን ጨርሳ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ተሸጋግራለች። ተናፋቂው የዓለም ዋንጫ በሩሲያ በመዘጋጀቱ የተለያዩ ውዝግቦች ሲነሱ የቆዩ ቢሆንም የቭላድሚር ፑቲን አገር የቤት ስራዋን ጨርሳለች። በተለይም ከአገሪቱ ነውጠኛ ደጋፊዎች ጋር በተያያዘ የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ከፍተኛ የዘረኝነት ድባብ ያንዣበበት ተደርጎ ተቆጥሯል። ሞስኮም ይህን ስጋት ለማስቀረትና የዓለም ዋንጫው ከስጋት ነፃ ሆኖ በስኬት ይጠናቀቅ ዘንድ ነውጠኛ የሆኑ ደጋፊዎቿን ሰብስባ በፊርማቸው ቃል እንዲገቡ እያደረገች ትገኛለች። ሩሲያ ለአንድ ወር በሚቆየው አውራ የእግር ኳስ ፍልሚያ የዓለም ሁሉ ትኩረት ማረፊያ ለመሆን ተሰናድታለች። ስታዲየሞችን ጨምሮ ካሰናዳቻቸው በርካታ መሰረተ ልማቶች መካከል ጥቂት እውነታዎችን እንደሚከተለው ቃኝተናል።
የዓለም ዋንጫውን በ12 ስታድየሞች የሚያስተናግዱት 11 የራሽያ ከተሞች ሲሆኑ እነሱም የመክፈቻ እና የዋንጫ ጨዋታዎች የሚካሄዱባትን መዲናዋን ሞስኮን ጨምሮ፤ ሴንት ፒተርስበርግ፤ ኤካተሪንበርግ፤ ካዛን፤ ሳማራ፤ ቮልጎጋርድ፤ ኒዛኒ ኖቮግሮድ፤ ሳርናሳክ፤ ሮስቶቭ ኦን ዶን፤ ካሊንኢንግራድና ሶቺ ናቸው፡፡ በእነዚህ 11 ከተሞች ከ25 ሚሊዮን በላይ ራሽያውያን እንደሚኖር መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የዓለም ዋንጫው 12 ስታድየሞች በድምሩ ከ550ሺ በላይ ተመልካቾችን ያስተናግዳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 12ቱም ስታድየሞች ከዓለም ዋንጫ በኋላ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እንዲሰጡ በጥንቃቄ ታስቦባቸው የተዘጋጁ ሲሆን 3 ስታድየሞች በውድድሩ ማግስት የሚያስተናግዱትን የተመልካች ብዛት ከ45ሺ ወደ 30ሺ ይቀንሳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከዘጠና ስድስት በላይ የስልጠና እና የልምምድ ማዕከሎች በአዲስ መልክ የተገነቡ ሲሆን ከዓለም ዋንጫው በኋላ ለ16ሺ ታዳጊዎች አገልግሎት እንዲሰጡ የታሰቡ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ዓለም ዋንጫው ከ100ሺ ለሚልቁ ሰዎች የስራ እድሎችን ፈጥሯል፡፡ በተለይ በ10 ስታድየሞች ግንባታ እና እድሳት 13ሺ የሩሲያ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡
የመክፈቻና የዋንጫ ጨዋታዎችን ጨምሮ 7 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን የሚያስተናግዱ ሲሆን በሞስኮ ከተማ ይገኛል። እኤአ በ2013 81ሺ ተመልካች የመያዝ አቅም እንዲኖረው ተደርጎም ታድሷል። ሌላው በሞስኮ ከተማ የሚገኘው ስታድየም የሩሲያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ የሆነው የስፓርታክ ሞስኮ ክለብ ሜዳ ሲሆን 4 የምድብ ጨዋታዎችና 1 የጥሎ ማለፍ ግጥሚያ እንደሚካሄድበት ይጠበቃል፡፡ ‹‹ዘ ማዘርላንድ ኮልስ›› ተብሎ የሚጠራው የዓለማችን ግዙፍ ሃውልት በሚገኝበት የቮልጎጋርድ ከተማ በቀድሞ ስሙ ስታሊንግራድ 4 የምድብ ጨዋታዎችን የሚያስተናግደው ይህ ስታድየም ከፍተኛ ነውጥ የሚያነሱ ደጋፊዎች ያሉበት እንደሆነም ይነገራል።
ከታዋቂው የራሽያ ወንዝ ቮልጋ የሚዋሰነው የሮስቶቭ ስታድየም 45ሺ ተመልካች የሚያስተናግድ ሲሆን በዓለም ዋንጫው አንድ የጥሎ ማለፍ ጨዋታና 4 የምድብ ጨዋታዎች ይካሄዱበታል፡፡ 1 ሚሊዮን ህዝብ የሚኖርበት የሮስቶቭ ኦን ዶን ከተማ የሩሲያ የትራንስፖርት መናኸሪያ ሲሆን ከዩክሬን ጋ በሚያዋስነው ድንበር አቅራቢያ ይገኛል፡፡
ሰላሳ አምስት ሺ ተመልካች የሚይዘው የኢካተሪናበርግ ስታድየም በ1950 እኤአ ላይ የተገነባ እና ለዓለም ዋንጫ በልዩ እድሳት የተዘጋጀ ሲሆን 4 የምድብ ጨዋታዎችን የሚያስተናግድ ይሆናል፡፡ ኢካተሪና በርግ ሩሲያን ከአውሮፓ እና ከኤሽያ ጋር በሚያገናኙ አውራ ጎዳናዎች እና አዋሳኝ ድንበሮች ላይ የተመሰረተች ከተማ መሆኗ ይታወቃል።
ሳማራ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ስታድየም 1 የጥሎ ማለፍ፤ 1 የሩብ ፍፃሜና 4 የምድብ ጨዋታዎችን የሚያስተናግድ ነው፡፡ በቮልጋ ወንዝ ላይ የተመሰረተው ይህ ከተማ ከሞስኮ በደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ 850 ኪሎ ሜትር ላይ የሚገኝ ሲሆን የሩሲያ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ የሚንቀሳቀስበት ነው፡፡
የሳርናሳክ ከተማ ከሞስኮ በደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ 500 ኪሎ ሜትር ላይ የሚገኝ ሲሆን በዓለም ዋንጫው 4 የምድብ ጨዋታዎችን የሚያስተናግደው ስታድየም እና አዲስ የተገነባ ነው፡፡
ዛቢቫካ ይህ የተኩላ ዝርያ የዓለም ዋንጫ የገድ ምልክት የሆነ እንስሳ ነው፡፡ የሰራችው ኤካተሪና ቦችሮቫ የተባለች የስነህንፃ ዲዛይን ተማሪ ስትሆን በድረገፅ የተካሄደ ምርጫን አሸንፋ በታለች፡፡
የዓለም ዋንጫውን እንግዶች ለማስተናበር የሚሰማሩት በጎ ፍቃደኞች በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ ናቸው፡፡16 የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰሩ ማዕከሎች የተገነቡ ሲሆን በዓለም ዋንጫው እንግዶች የሚሆኑ ከ1 ሚሊዮን በላይ ስፖርት አፍቃሪዎችን ለማስተናገድ የሚሰማሩት ከ25ሺ በላይ በጎ ፈቃደኞች ናቸው፡፡
ለዓለም ዋንጫው 26 የትራንስፖርት መሰረተ ልማቶች ተገንብተዋል፡፡ 11 የአየር ማረፊያ ጣቢያዎች አዲስና በእድሳት ተገንብተዋል፡፡ አዳዲስ የአየር ማረፊያዎች በሴንት ፒተርስበርግ ፤ በኒዚሂ ኖቭጎሮድ፤ በሳናራ፤ ሳርሳንካ እና ሞስኮ ከተሞች ተሰርተዋል፡፡ በሮስቶቭ ኦን አዲስ የአየር ማረፊያ ጣቢያ ሙለሙሉ ተሰርቶ ተጠናቋል፡፡
ሦስት አዳዲስ የሜትሮ ባቡር ጣቢያዎች፤ 12 አውራ ጎዳናዎች እና ማሳለጫ መንገዶች ተዘርግተዋል፡፡
በአዲስ መልክ የተገነቡ እና ሙሉ እድሳት የተደረገላቸው 13 ሆስፒታሎች፤ 29 የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ተቋማት፤ 27 አዳዲስ ሆቴሎች፤ 12 የኤሌክትሪክ ኃይል ማሰራጫ ጣቢያዎች ተሰርተዋል፡፡ ስምንት መቶ ሄክታር የህዝብ መናፈሻዎች እና ፓርኮችም የዓለም ዋንጫውን ምቹና የተሳካ ለማድረግ ተዘጋጅተዋል፡፡

ቦጋለ አበበ

 

 

Published in ስፖርት
Saturday, 12 May 2018 18:15

ጨምሯል!

አዛውንቱ ጋሽ ወርቁ አራት ልጆቻቸውን ድረው ትንሿ ሀሴት ብቻ ቀርታቸዋለች። ባለቤታቸው ወይዘሮ እጅግአየሁ እንደእርሳቸው እርጅና ስላልተጫጫናቸው ንቁ ዓይንና ጆሮዎች አሏቸው። ጋሼ ወርቁ ረጅም ዘመን በብረታ ብረት ሥራ የኖሩ በመሆናቸው ጆሯቸው ማዳገም ከጀመረ አስር ዓመት አልፏቸዋል፤ ቀረብ ብለው ካልነገሯቸው አይሰሙም። ጡረታ ባይኖራቸውም በደህና ቀን ያፈሩት ጥሪት የሽምግልና ዘመናቸውን አላከበደባቸውም። ሲሰራ የኖረ መቀመጥ አይወድም! ይባል የለ? እርሳቸውም የግቢ አትክልት ከመኮትኮት፣ በተስኪያን ከመሳለም የተረፈ ጊዜያቸውን ልጆቻቸውንና የልጅ ልጆቻቸውን በመጎብኘት ያሳልፋሉ። በየዓመቱ ለግንቦት ልደታ ደግሞ የጋሼ ወርቁ ልጆች ብቻ ሳይሆኑ ጎረቤት ዘመድ አዝማድ ሁሉ ተሰባስቦ የሚያመሸው እርሳቸው ግቢ ነው። በዚህ ቀን የሚጠራም፣ የሚቀርም የለም፤ ሁሉም ቀኗን ቆጥሮ ቀጠሮ ሰርዞ ይገኛል። ጨዋታው፣ ቀልዱ፣ ወሬው፣... እስከ አምስትና ስድስት ሰዓት ደርቶ ይቆያል።
የትናንት በስቲያ ማምሻም እንደድሮው ነበር። ከረፋዱ ጀምሮ ቤቱ በግርግር ተሞልቷል። አመሻሹ ላይ ግቢው በሰው ተሞላ። ከለስላሳ እስከ ጠላ ብሎም እስከ አረቄ የማይቀዳ መጠጥ የለም። ወጣቱ ለብቻ፤ ሴቶች አዛውንቶችና ሕፃናት ያለፈ ዓመት አከራረማቸውን የቀጣይ ዓመት እቅዳቸውን በሙሉ የሚለዋወጡት በዚህ ቀን ነው። የለመደ ቀኑን ይናፍቀዋል፤ ይቀጣጠርበታል፤ ዓመት ዓመቱ አድርሰን ብሎም ይመራረቅበታል። ሥርዓት ወጥቶለት ዓመት ተጠብቆ ይከበራል። ግንቦት ልደታ በጋሽ ወርቁ ግቢ።
ታዲያ በዓሉ የምግብና የመጠጥ ብቻ ሳይሆን የአቀማመጥም ሥርዓት አለው። በእንጨት ከለላ በተሰራላት በረንዳ ውስጥ ወይዘሮ እጅግአየሁ እንደእርሳቸው በእርጅና መንገድ ካሉ ሁለት ጎረቤቶቻቸው ጋር በስኒ የተጠቀጠቀ ረከቦታቸውን ዘርግተው ይታያሉ። የቀጤማው ጉዝ ጓዝ ፣ ጭሳ ጭሱ፣ ፈንድሻው ከለበሱት ነጭ የሀገር ባህል ልብስ ጋር የማያልፍ ትዝታን ያጭራል። ከበረንዳው ስር በስተቀኝ ጋሽ ወርቁ ረጅም ጋቢ ለብሰው ተቀምጠዋል፤ እየቆዩ ትክዝ፣ ፍዝዝ ይላሉ። አዲስ ነገር ባይኖርም የጎደለ ግን አለ። እስከ ዛሬ ይህን ቀን ከጎናቸው የማይለዩዋቸው ሻምበል ባሻ ደሬሳና አቶ አለሙ ወርቅአፈራሁ ዛሬ የሉም። ነፍሳቸውን ፈጣሪ በአፀደ ነፍስ ያኑረውና ተከታትለው ወደማይቀርበት ሄደዋል። ዛሬ በእነርሱ ምትክ በዕድሜ ባይስተካከሏቸውም ባገቡና በወለዱ ጎልማሶች ተከበዋል።
የጋሽ ወርቁ ዓይን ከወዲህ ወዲያ ይባዝናል። እልፍ ብሎ በመናፈሻ ውስጥ እጃቸውን እያወናጨፉ የሚንጫጩት የሰፈር ወጣቶች ድምፅ ከአለፍ አገደም ይሰማቸዋል። ከወንዶቹ አጠገብ ሦስቱ ሴት የልጅ ልጆቻቸው እኩዮቻቸው ከሚሆኑ የሰፈር ሴቶች ጋር ቀዝቀዝ ያለ ጨዋታ ይዘዋል። ከጀርባቸው ወሰን ያስከብርልኛል ብለው ከተከሉትና ረጅም ዘመን ካሳለፈው ጽድ ስር የተነጠፈላቸው ጅባ ላይ ንፍሮና ዳቦ እየተናጠቁ የሚጫወቱ ሕፃናቶች አሉ።
ጋሽ ወርቁ ከአጠገባቸው የራቁትን ታዳሚዎች ጨዋታ ለመስማት ባይታደሉም ልጆቻቸውን ጨምሮ የከበቧቸውን ግን ከአፋቸው የወጣውን ሁሉ እያዳመጡ ነበር። ኧረ ምን ማዳመጥ ብቻ በየሮሯቸውም መሀል ጭልጥ ብለው ዓመታትን ወደኋላ በሃሳብ ይነጉዳሉ።
ወሬያቸው ሁሉ የኑሮ ውድነት ነው። ወተት እናንተ ሰፈር አለ? አንዷ ትጠይቃለች። ከየት መጥቶ ከሥራ ስመለስ ነው እየገዛሁ የምገባው። ግማሹን ሊትር አስራ አምስት ብር ይላሉ፤ በዛላይ ቶሎ ካልደረሱ ያልቃል። ልጆቹ ደግሞ ወተት ከሌለ የቀረበው ሁሉ እህል አይመስላቸውም፤ ትንሿማ ጭራሽ አትነካውም። ደግሞ አንዳንዴ ስታፈይው ይበጣጠሳል።...የምሬቱ ወሬ ደርቷል።
ጋሽ ወርቁ ዓመታትን ወደኋላ ተመለሱ። አራቱን ልጆታቸውን ያሳደጉት ከወይዘሮ የወዲያነሽ ወተት እየተከራዩ ነበር። ሊትር ሃያ ብር፣ ግማሽ አስር ብር፣ ቡትሌ ስድስት ብር አይረሱትም። ይሄ እንግዲህ በወር ነው። ደግሞ መስፈሪያ አይጠበቅም ነበር ማለት ከተሰፈረ በኋላ መረቅ ይደረግበታል። ጥራቱስ ቢሆን ቢያድር ድፎ ዳቦ የሆነ እርጎ ይወጣዋል እንጂ መበጣጠስ የሚባል ነገር አያውቅም። ጥሬውን ቢጠጡት እንኳ ምግብ ነው፤ ወተት ጠጥቶ ቆረጠኝ የለ፣ ፈለጠኝ።
እኔማ ለከርሞ አፄ ናኦድ ነው የማስገባው። የመንግሥት ትምህርት ቤት። ሦስት መቶ ብር ባንዴ እንዴት ይጨመራሉ? በዚያ ላይ ስድብ ነው ተምረው የሚመጡት። ሲታዘዙ፣ ሲጠየቁ፣ ሲመከሩ መልሳቸው «መብቴ ነው» ነው። ምን ሊረባ አለች ትልቋ ልጃቸው ምርር ብላ። ወይ ጉድ! ጋሽ ወርቁ ወደ ሌላ ዓለም ተሻገሩ ምን ጊዜ መጣ? እኛ በነሐሴ አስመዝግበን ዞር ነበር የምንለው። ደብተርም አንዳንዴ ነው የምገዛው፣ በመሀከሉ እንዲህ ቢሉም ባመት አንዴ ነው የሚገዛው። እስኪብርቶም ቢሆን ካልጠፋ ወይንም ካልተሰረቁ ወር ይቆያል። እርሳስ ፣ላፒስ... ኧረ! እንዲህ ተማረን አናውቅም ፤ ከራሳቸው ጋር ያወጋሉ።
የእድምተኛው ጨዋታ የጋሽ ወርቁም ትዝታ ቀጥሏል !!!
የዱቄቱን ሰማሽ? አይገርምም ማካሮኒና ፓስታም እኮ ጨምሯል? የስኳርና የዘይቱን ዝም ስንል እያደር መጫወቻ አረጉን፤ ሌላ የእሮሮ ርዕስ ተከፈተ። ጋሽ ወርቁ የማጀት ዕቃ የገዙበትን ቀን አያስታውሱም ግን በአርባ አምስት ዓመት የትዳር ጉዟቸው ባለቤታቸው ወይዘሮ እጅግአየሁም ቢሆኑ እንዲህ ሲያማርሩ ሰምተው አያውቁም። ድንገት ሌላ ሃሳብ ሌላ ጭንቀት ድቅን አለባቸው። ጉድ እኮ ነው! ለእጅግአየሁ ብሎ ገበያ የሚቀንስ የለ፤ የሸቀጥ ዋጋ ሁሉ ሽቅብ ወጣ ብዬ ስነግረው ግፊቱ ይጨምራል ብላ ደብቃኝ ኖራ ይሆናል እንጂ። አዬ ጉድ እንደው ይሄን አምጪ፤ ይሄን ጨምሪ ስል ሰንብቼ እቴን እንዴት ሳስቸግራት ኖሯል!?። የባለቤታቸው ዝምታ በጸጥታ ውስጥ ያለ ጩኸት ሆኖ ተሰማቸው።
በተከፈተው መዝሙርና ጫጫታ ግቢው ደምቋል። ለጋሽ ወርቁ ግን የሚሰማቸው ከኑሮ ውድነት ጋር የሚወራው ምሬት አዘል ብሶት ብቻ ነው። ስንቱን ጉድ አነሱት። እነዚህ ልጆች እንዲያው ቆመው መሄዳቸው አሉ የሰው ሁሉ ችግር ተደራርቦ እየተሰ ማቸው።
ከልጃቸው የማይለዩዋት የክፉ ቀን ወዳጃቸው የሻምበል ባሻ ደሬሳ ልጅ ትሁኔ ያነሳችው እሮሮ ግን ሁሉንም ያለአዳማጭ እንዲንጫጩ አደረጋቸው። የቤት ኪራይ። ሁሉም ያወራል። ዋጋ በየወቅቱ ይጨመራል። ውሃ ይቆለፋል፣ በር ይዘጋል፣ መፀዳጃ ቤቱ...
እነዚህ ልጆች የሰው ቤት ነው ተከራይተው ያሉት? ጋሽ ወርቁ ራሳቸውን ጠየቁ።
ድሮም አከራይ መቆጣቱ አይቀርም ግን እንዲህ አይከፋም ነበር።
ሌላ ትዝታ በጋሽ ወርቁ ህሊና መጣ። የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ የሚሉ ጋዜጦች በተለጠፉበት ሳጠራ ለሁለት በተከፈለ ሰፊ የድሮ ሳሎን ውስጥ ከገጠር ሲመጡ በደባልነት ያሳለፉትን ሁለት ዓመት በድጋሜ መለስ ብለው አስታወሱ። በአንድ በር ገብተው፣ ከአንድ ድስት ተቃምሰው በሲባጎ በተወጠረ መጋረጃ መኝታ ክፍላቸውን ለይተው ኖረዋል። ፍቅር ምን ይገድበዋል። እንደዚያ በአየር ተለያይተውም ሲመሽ ደህና እደሩ፤ ሲነጋ እንዴት አደራችሁ... እግዚአብሔር ይመስገን ይባባሉ ነበር። ውሃው ከቦኖ፣ መብራቱም ያን ያህል የከፋ አልነበረም።
አቤት ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋል እንዲሉ። በብቻ የትውስታ ጨዋታቸው ጭለጥ ብለው ሄዱ። ደግሞ መለስ አሉ ግቢው ጭር እንዳይል ብለው ያከራዩት የኔነህ በህሊናቸው መጣ። ጠላውን እያሳበ ይጫወት ይዟል።
አስቸግሬው ይሆን እንዴ ? ራሳቸውን ጠየቁ።
መቼ ወጣህ? መቼ ገባህ አልለው? ማን መጣ ብየውም አላውቅ፤ ሦስት ዓመት ሙሉ ሃምሳ ሳንቲም አልጨመርኩ። ባለፈውም ያገር ዋጋ ነው አታስጨንቁኝ ሲለኝ ነው የራሱን ጭማሪ የተቀበልኩት። ለዚያውስ ምን ያህል ጨምሮ። ጋሽ ወርቁ በትንንሽ ዓይኖቻቸው የኔነህን እያዩ በሃሳብ ከነጎዱበት የመቁረጫ ልጃቸው ሀሴት ድምጽ አናጠፋቸው።
ሀሴት ለሠርጓ ዝግጅት የገጠማትን ሰነዘረች።
እኔማ በዚህ እሳት ዘመን ሠርግ አስቤ ወርቁም ጨመረ እኮ!
እሱም ጨመረ? የሁለት ታላቅ እህቷ ጥያቄ ነበር።
ከቤት ኪራዩ ሃሳብ ያልወጡት ጋሽ ወርቁ በሚያዳግም ጆሯቸው ለሰሙት ሮሮ ጣልቃ ገብተው መልስ ሰጡ፤
ኧረ! እኔ አልጨመርኩም? ምን ሆናችኋል! ኩነኔ አትክተቱኝ። ከዚህ በኋላ ምን ላደርግበት ምንስ ቀረኝና ነው። አሉ ግራ በመጋባት።
ሁሉም ከትብለው ከልባቸው ሳቁ።
ጋሼ! ወርቁ እኮ ያልንህ ቀለበት ለማሰራት ነው። አንተን አይደለም። ሀሴት መለሰች።
ጋሽ ወርቁ ፈገግ አሉ። በዚያውም ደስ አላቸው በልጆቻቸውም ኮሩ።
በልባቸውም ተመስገን ፈጣሪዬ አሉ። እንዲህ ችግር ተደራርቦባቸው፣ የችግር ጉም ከቧቸው የሚስቁ ልጆች በማፍራታቸው።
ሳይደግስ አይጣላም ጨምረው አመሰገኑ ጋሽ ወርቁ። ይሄው የኔ አባት ዛሬም ችግሩን ብቻ ሳይሆን መከራውንም የሚችልበት ደንዳና ትከሻ ለትውልዱ ሰጥቶታል።
ሦስተኛ ተመስገን አሉ ፍጹም ከልባቸው። ለካ ችግሩ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር እንደ ሕዝብ ትዕግስቱም መቻሉም ጨምሯል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

Published in መዝናኛ

የኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀጽ ሰላሳ አራት የጋብቻ የግልና የቤተሰብ መብቶችን አስመልክቶ ባሰፈረው ነጥብ ጋብቻ በተጋቢዎች ነጻና ሙሉ ፍላጎት ላይ ብቻ ይመሰረታል ሲል ይደነግጋል። የዚህ ድንጋጌ ሃሳብ እንደሚገልጸውም ማንኛውም ሰው ከፍላጎቱ ውጪ በማንም አስገዳጅነት ተጽዕኖ ስር መውደቅ እንደማይ ኖርበት ነው።
ህጻናት የህብረተሰቡ አንድ ክፍል እንደመ ሆናቸውም በህገመንግስቱ አንቀጽ ሰላሳ ስድስት ላይ የሰፈረ ሙሉ መብትና ነጻነት ተሰጥቷቸዋል። በዚህ ድንጋጌ መሰረትም ህጻናት በህይወት ከመኖር ጀምሮ የመማር፣ስምና ዜግነት የማግኘት፣ጉልበትን ከሚበዘብዙ ልማዶች የመጠበቅ መብት አላቸው። ከነዚህ የማይጣሱ መብቶች በተጨማሪ በጤናቸውና በደህንነታቸው ላይ ጉዳት ከሚያደርሱ ተግባራት ይጠበቁ ዘንድ የህግ ከለላ ተሰጥቷቸዋል።
ሀገሪቱ ህገመንግስት የህጻናት ደህንነትና ሰብአዊ መብት በአግባቡ እንዲጠበቅ በህግ ያሰፈረ ቢሆንም ብዙ ጊዜ ግን እነ
ዚህ መብቶች የሚጣሱበትና የማይተገበሩበት እውነታ ጎልቶ ይስተዋላል። ከእነዚህ የህግ ጥሰቶች መካከልም ህጻናትን ያለዕድሜያቸው አስገድዶ መዳር አንዱና ዋነኛው ነው። ጋብቻ እንደ የአካባቢው ባህል፣ ሃይማኖትና ልማድ መነሻነት ይመሰረታል። ሲመሰረት ግን የተጋቢዎችን ዕድሜና ፍላጎት ያላገናዘበ ከሆነ ስነልቦናዊ ጉዳትን ጨምሮ ጤንነትን እስከማሳጣት የሚዘልቅ የከፋ ተጽዕኖ ሊያስከትል ይችላል።
እንደ ሴቭ ዘቺልድረንና የዓለም ባንክ እአአ የ2016 መረጃዎች መሰረት በዓለማችን በየቀኑ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ልጃገረዶችና ህጻናት ያለዕድሜያቸው ይዳራሉ። በእንዲህ አይነቶቹ ጋብቻዎች ምክንያትም በርካታ የሚባሉ ተጽዕኖዎች እየደረሱ ነው። የጋብቻ ዕድሜ መለያ እንደየሀገራቱ ህገመንግስት ድንጋጌ የተለየ ቢሆንም እነዚህ ህጎች በዘፈቀደ የሚጣሱ መሆናቸው ግን ህጻናትን ያለዕድሜያቸው በማስገደድ የጋብቻ ቀንበርን እንዲሸከሙ እያደረጋቸው ነው።
የህጻናትን መብት በህገመንግስታችን አስፍረናል በሚሉ ሀገራት ብቻ በየአመቱ ወደ 7 ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናት ያለዕድሜያቸው ጋብቻን እንዲፈጽሙ ይደረጋል። በሀገራቸው የህግ ከለላ የማይደረግላቸው አንድ መቶ ሚሊዮን ህጻናትና ልጃገረዶችም ወደጋብቻ ህይወት እንዲገቡ ይገደዳሉ። ይህ እውነታ ከሚተገበርባቸው አህጉራት መካከልም የማዕከላዊና ምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ።
ህጻናትን ያለዕድሜያቸው የመዳር አስገዳጅነት ዓለምአቀፉን የህጻናት መብትን ፈርማ በተቀበለችውና በህገመንግስቷም ላይ ባሰፈረችው ኢትዮጵያ ጭምር የሚስተዋል እውነታ ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ አሳሳቢነቱን በእጅጉ የሚያጎላው ይሆናል። መረጃዎቹ እንደሚጠቁሙት አሁንም ድረስ በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ያለዕድሜ ጋብቻዎች ይፈጸማሉ። ከሶስት ልጃገረዶች አንዷ ከአስራ ስምንት አመቷ በፊት ጋብቻ የምትመሰርት ሲሆን በዚህ ዕድሜ ክልል በትዳር ህይወት ውስጥ የሚገኙት ሴቶችም ሰላሳ ስድስት በመቶውን የሚሸፍኑ መሆናቸው ተረጋግጧል። እነዚህ ህጻናት በአብዛኛው ወደጋብቻ እንዲገቡ የሆኑት በአካባቢው ባህልና ነባር ወግ አስገዳጅነት ነው። ይህም ለአመታት በህብረተሰቡ ማንነት ውስጥ ሰርጾ የኖረና በአጭር ጊዜ ሊወገድ የማይችል ጎጂ ልማድ መሆኑ ይታወቃል።
በቅርቡ በመዲናችን አዲስ አበባ ካፒታል ሆቴል በተደረገ ቆይታ ይህንኑ ርዕሰ ጉዳይ መነሻ ያደረገ ውይይት ተካሂዷል። በዕለቱ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማትና ከዓለም ባንክ ከተገኙ ባለሙያዎች ጋር በነበረው ምክክር የህጻናት ጋብቻና የሚያስከትለው
ሀገራዊ ተጽዕኖ በስፋት ተዳሷል።

ያለዕድሜ ጋብቻ መልከ ብዙተጽዕኖዎች እንዳሏቸው የሚጠቅሱት በዓለም ባንክ የኢኮኖሚስት ዘርፍ ሃላፊው ዶክተር ኪዩንቲን ቲዎዶን ተጽዕኖዎች በግለሰቦች ብቻ ሳይሆን በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጭምር ጉዳት እንደሚያስከትሉ ይናገራሉ። እንደ ዶክተር ኪዩንቲን አባባል ያለዕድሜ ጋብቻ ያልተመጣጠነ የህዝብ ቁጥር ማስከተልን ጨምሮ ለጤንነት መቃወስንና ለምግብ እጥረት መኖር አይነተኛ ምክንያቶች ይሆናሉ።
በተለያዩ ስፍራዎች ያለዕድሜ ጋብቻ መስፋፋት ልጆች መማር በሚገባቸው ዕድሜ ወደትምህርት ቤት እንዳይሄዱና እስከዘለቄታውም የቀለምን ጥቅም ሳያውቁ እንዲቀጥሉ የማድረግ ተጽዕኖው የሰፋ ነው። በለጋ ዕድሜያቸው በስራ ተጠምደው ቤተሰብን የማስተዳደር ቀንበር እንዲሸከሙም ያደርጋል። ይህ መሆኑ ደግሞ አምራች ዜጎችና ውሳኔ ሰጪዎች እንዳይሆኑ ያደርጋል።
በአሁኑ ጊዜ ዓለማችንን እየፈተናት ባለው የኤችአይቪ/ ኤድስ በሽታ ተጋላጭ የመሆን ዕድላቸውንም ያሰፋዋል የሚሉት ሃላፊው ከዚህ አንጻር ሀገርን በኢኮኖሚው ዘርፍ ሊያስከፍል የሚችለው ዋጋ እጅግ የገዘፈ እንደሚሆን ጥናቱን ዋቢ አድርገው ያስቀምጣሉ።
በኢትዮጵያም ቢሆን ይኼው ማህበራዊ ተጽዕኖ ስር ሰዶ መቆየቱን በስጋት የሚያስተውሉት ዶክተር ኪዮንቲን ልጃገረዶች ገና በለጋው ዕድሜያቸው ለጋብቻ እንዲሰጡ የመደረጉ እውነት ባህላዊ መሰረቱ የሰፋ ነውና በቀላሉ ለማስቀረት ያልተቻለበትን ተሞክሮ ይጠቅሳሉ። ይህ በመሆኑም ባልጠነከረ አካልና ልጅ ለመውለድ ባልተዘጋጀ ስነልቦና እናትነትን ለመቀበል መዘጋጀት የሚኖረውን ችግር የከፋ ያደርገዋል ይላሉ።
በሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች ጉዳይ ተሳትፎና ንቅናቄ ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ታደሰ ያለዕድሜ ጋብቻ በትምህርት፣በጤና፣በስነህዝብና በውሳኔ ሰጪነት ረገድ እያስከተለ ያለው ክፍተት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ስለመሆኑ ይናገራሉ። በሀገራችን ተገቢውን የስራ ዕድል ለማግኘት እንዳይቻል በሚኖረው መነሻነት እስከ ሀገር ኢኮኖሚ የሚዘልቅ ተጽዕኖ እንዲፈጠር ያደርጋል። ከጥንት ጀምሮ ተያይዞ የቀጠለው ያለዕድሜ ጋብቻ ቢቆም ምን አይነት ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል? የሚለውም ጥናታዊ ዳሰሳ ተደርጎበታል።
እንደ አቶ ስለሺ አባባል የዓለም ባንክ ተጽዕኖዎቹን ለይቶ ባቀረበው መሰረት የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴርም በአራት ዘርፎች ላይ ትኩረት በመስጠት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። በመጀመሪያ ጥናቱ ሲካሄድ ዓለም አቀፋዊ ደረጃውን የጠበቀ መሆን ስለሚኖርበትም ለመረጃው ትክክለኛነት ትኩረት ተሰጥቶበታል። በዚህም ረገድ የጥናት ዘዴዎቹ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የፍተሻ መስመር እንዲያልፉ ተደርጓል።
የዓለም ባንክ ያለዕድሜ ጋብቻን በተመለከተ ጥናት ለማድረግ ከመረጧቸው ሀገራት መሀል ሀገራችን አንዷ ለመሆን ችላለች። ለዚህም መመረጥ መነሻ የሆነው በተለያዩ አካባቢዎች ለግርዛትና ያለዕድሜ ጋብቻ የተሰጠው ትኩረትና ችግሮቹን ለመታደግ በሚደረገው ጥረት ስለመሆኑ ዳይሬክተሩ ይናገራሉ። ጥናቱን መነሻ አድርጎ ወደፊት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ለመለየት አጋጣሚው መሰረት እንደሚሆንም መተማመኛ ተሰጥቷል።
እንደ አቶ ስለሺ አገላለጽ በአሁኑ ጊዜ እንደቀድሞው የከፋና ለመቆጣጠር የሚያዳግት ያለዕድሜ ጋብቻ ይከናወናል ለማለት አያስደፍርም። ለዚህም ማሳያ በ2016 የወጣው ስታስቲክስ መረጃ ጋብቻው በተለይም ከ18 ዓመት በታች በሆኑ ህጻናት ላይ እየቀነሰ ስለመሆኑ ያመላክታል። ይሁን እንጂ እነዚህ ውጤቶች መታየታቸው ብቻ ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ተወግዷል የሚያስብል አይሆንምና ጥረት የማድረጉ እንቅስቃሴውን ግድ እንዲል ያደርገዋል።
አቶ ስለሺ ቀደም ሲል በሀገራችን ጎልቶ ይታይ ለነበረው ያለዕድሜ ጋብቻ መቀነስ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን አስመልክቶ የተቀረጹ ፖሊሲዎችን እንደዋንኛ ምክንያት ያስቀምጣሉ። እነሱን መሰረት አድርገው የተቋቋሙ ብሄራዊ ጥምረቶችም ግንዛቤን በመፍጠር በኩል ያላቸው አስተዋጽኦ የላቀ ነው። በየክልሉ የተዋቀሩ ተመሳሳይ አደረጃጀቶችም ድርጊቱን ለመቀነስ ያደረጉት ሚና ቀላል የሚባል አይደለም። ከሁሉም በላይ ደግሞ በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶችን የማስወገድ የድርጊት መርሀ ግብር መካተቱ ለእንቅስቃሴው ስኬታማነት የጎላ ድርሻ አበርክቷል።
የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴርም ሀገራዊ ንቅናቄን በመፍጠር ካለዕድሜ ጋብቻን ጨምሮ ከግርዛትና ሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ነጻ ለወጡ አካባቢዎች ዕውቅና እየሰጠ ይገኛል። ከጥቂት ጊዜያት በኋላ በሀገሪቱ ተግባራዊ የሚሆን የፍኖተ ካርታ ዝግጅትም ተጠናቋል። ይህ የዕቅድ ዝግጅት ዓለምአቀፋዊ ብቃትን የያዘ ሲሆን አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ማካተት የሚያስችልና የልማት ቡድኖችን የሚያወቅር አደረጃጀት እንደሚኖረውም አቶ ስለሺ ይናገራሉ።
ያለዕድሜ ጋብቻ በአንድ ዜጋ ላይ ከሚያስከትለው የተናጠል ተጽዕኖ ባሻገር በሀገር ገጽታና ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ተግዳሮት ቀላል የሚባል አይደለም። በትምህርት፣ በጤና፣ በስነህዝብና በተለያዩ የስራ ዕድሎች መቀነስ ዙሪያ የሚኖረው ማነቆም ሀገር በተሻለ ፍጥት እንዳትጓዝና ካደጉ ሀገራት ተርታ እንዳትሰለፍ ያስገድዳል። ህዝብን ይዞ ጉዞ ባለበት የልማት እርምጃ መሀልም እንዲህ አይነቱ የጎጂ ባህሎች እንቅፋት መኖር ተገቢ አይሆንምና ሁሉም ለችግሩ መወገድ ክንዱን ሊያበረታ ይገባል።

መልካምስራ አፈወርቅ

Published in ማህበራዊ

በአንዳንድ የክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ድሮም ጀምሮ በግጦሽ መሬት፣ በውሃ፣ በጎሳ አለመስማማት ላይ የተመሰረቱ ግጭቶች ይከሰታሉ። ይሄ ወደፊትም ሊከሰት ይችላል። ሆኖም ግን ችግሩ ቶሎ መፍትሔ ከተሰጠው አንዳንዴም መልካም ነገር እንዳለው የዛሬው እንግዳችን በአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብትና የፌዴራሊዝም መምህር ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ ይናገራሉ፡፡
የጋራ አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አለመሰጠቱ፣ ክልሎች ህገ መንግሥቱን አክብረው እንዲሄዱና ሁሉንም ታሳቢ አድርገው እንዲሠሩ አለመደረጉን እንደችግር ይጠቅሳሉ፡፡ በእነዚህና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቃለመጠይቅ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፦ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞችና ተፎካካሪ ፓርቲዎች «ከቋንቋ ይልቅ በጂኦግ ራፊና የህብረተሰብን አሰፋፈር ያማከለ ፌዴራ ሊዝምን መከተል ይገባል» ሲሉ ይደመጣል። በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
ዶክተር ሲሳይ፦ የፌዴራሊዝም ስርዓትን በመከተል ላይ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ገዢው ፓርቲ መግባባት ላይ መድረሳቸው አንዱ መልካም ነገር ነው፡፡ አተገባበሩ ላይ ብዙ ነገር ማንሳት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ የፌዴራል አደረጃጀቱ ሙሉ በሙሉ በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በህገ መንግሥቱ በግልጽ እንደሰፈረው በአሰፋፈር፣ በቋንቋ፣ በስነ ልቦና እና የህዝብ ውሳኔ ግምት ውስጥ ያስገባ ነው።
ይህም ሆኖ ባለፉት 27 ዓመታት ለቋንቋ ልዮነት የበለጠ ትኩረት ተሰጥቷል። ያንን ታሳቢ አድርጎ በቋንቋ ላይ መመስረቱ ብቻ ችግር አለበት በሚልም ይገለጻል። ያንን የሚቀይር የመፍትሔ ሃሳብ የማምጣት ጉዳይ ከተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሲነሳ ይሰማል፡፡ ይሄ መነሳቱ ጥሩና ጤናማ ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦችን፣ ጋምቤላን፣ የደቡብ ብሄሮችና ብሄረሰብ ህዝቦች ክልሎችን ማንሳት ይበቃል። 56 ብሄር ብሄረሰብ ባለበት ደቡብ ክልል ላይ የሥራ ቋንቋቸው አማርኛ ነው፡፡ በቤኒሻንል ጉሙዝ ክልል ነባሮቹን ብንወስድ እንኳን ከአምስት ያላነሱ ብሄር ብሄረሰቦች አሏቸው፡፡ አሁንም የሥራ ቋንቋቸው አማርኛ ነው፡፡ በርታ ወይንም ጉሙዝ ይሁን አላሉም፡፡ ስለዚህ ሊያግባባ የሚችል ነገር ግምት ውስጥ ማስገባት አንዱ ጥሩ ነገር ነው፡፡
ዋናው ነገር ሁለት ጉዳይ በአንድ ጊዜ ወደ ተግባር መጥቷል፡፡ የፌዴራሊዝም ስርዓት ያለዴሞክራሲ ሥራ ላይ አይውልም፡፡ ምክንያቱም የጋራ አመራርና የራስ አስተዳደርን ተግባራዊ ለማድረግ የሚፈቅድ በመሆኑ ነው፡፡ እነዚህን ለመተግበር ምርጫ ያስፈልጋል፡፡ ህዝቦች ራሳቸውን የሚመራቸው አካል መምረጥ አለባቸው፡፡ በጋራ አገሪቱን ለመምራትም መርጠው መወከል አለባቸው፡፡ ምርጫዎች ደግሞ በባህሪያቸው ዴሞክራሲያዊነትን ታሳቢ ያደርጋሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ግምት ውስጥ ገብተው ከታየ የፌዴራል ስርዓቱ ለኢትዮጵያ አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ነገር ግን አተገባበሩ ላይ አሁንም ችግሮች አሉ፡፡
ከችግሮቹ መካከል አንደኛው አሁንም የማንነት ጥያቄዎች አልተመለሱም፡፡ ሁለተኛ አሁን በታላላቅ ብሄር ብሄረሰቦች ላይ የተመሰረቱ ለክልሎች ባለቤት አድርጎ የመስጠት ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ የአማራ ክልል፣ የትግራይ ክልል ወይም የኦሮሚያ ክልል ይባሉና ክልሎቹ የዋና ዋና ብሄር ብሄረሰቦች ብቻ እንደሆኑ አድርጎ የማሰብ ነገር ይታያል፡፡ ለምሳሌ ነባሩ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ ላይ ደግሞ ለተወሰኑ ነባር ብሄረሰቦች ባለቤት አድርጎ በመስጠት ሌላው ህዝብ ባለቤት እንዳልሆነ ወይም እንደ መጤ የመቁጠር፣ እኩል ያለማሳተፍ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህ እንግዲህ በሂደት የሚስተካከሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
አዲስ ዘመን፦ እኩል ተሳትፎ ሲባል ምን ማለት ነው?
ዶክተር ሲሳይ፦ እኩል ተሳትፎ የሚባለው አንደኛው በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ሀብት እኩል የመጠቀም ጉዳይ ግምት ውስጥ መግባት አለበት፡፡ ይህንን በማድረግ ረገድ ለባለቤቶችና ለመጤዎች የመከፋፈል ነገር አለ፡፡ ከመሬት አቅርቦት፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣የትምህርት ዕድሎችን በአግባቡ ከመጠቀም ጋር ተያይዞ ዕኩል ተጠቃሚ ያለመሆን እዚህም እዚያም ቦታዎች ላይ ይታያሉ፡፡
ሌላው የሥልጣን ክፍፍል ነው፡፡ የፌዴራል ስርዓት ሲባል በክልል እና በፌዴራል የሥልጣን ክፍፍል ይኖራል። ከዚህም አልፎ በአንድ መዋቅር ላይ የሥልጣን ክፍፍል ይኖራል፡፡ የጎንዮሽና የላይና የበታች ተብሎ የሚወሰደው ማለት ነው፡፡ ክልሎች ላይ በሥልጣን ያለው ሁኔታ ሲታይ የተሟላና ፍትሐዊ የሥልጣን ክፍፍል አይስተዋልም፡፡ ነባር ለተባሉት ሥልጣኑን የማሳለፍ ነገር አለ፡፡ ስለዚህ የሥልጣን ክፍፍሉ ፍትሐዊ መሆን አለበት፡፡ በክልሎች ውስጥ ያሉት ብሄር ብሄረሰቦች ውክልናቸው በትክክል መረጋገጥ አለበት፡፡ ውክልና ሲባል በፌዴራል መንግሥት፣ በክልል፣ በዞን፣ በወረዳ እስከ ቀበሌ ድረስ እኩል መሳተፍ ይኖርባቸዋል፡፡ አሁን ይህንን በሚያረጋግጥ መልኩ ተግባራዊ ባለመደረጉ መስተካከልና መታረም አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፦ የማንነት ጥያቄዎች አሁንም ምላሽ አላገኙም ይባላል። ይሄ ምን ማለት ነው? ዶክተር ሲሳይ፦ ይህ ማለት ህገ መንግሥቱ ግልጽ ነው፡፡ በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 ንዑስ ቁጥር ሁለት መሰረት በክልሎች ውስጥ ያሉ ብሄር ብሄረሰቦች በማንኛውም ጊዜ የራሳቸውን ክልል ማቋቋም ይችላሉ፡፡ ይህ አሁን እየተከበረ አይደለም፡፡ ማንነታችን ይሄ ነው እያሉ አይደላችሁም ተብለው የሚከለከሉበት ሁኔታ ትክክል አይደለም፡፡ ይህ ፍትሐዊም፣ ዴሞክራሲያዊም፣ ህገ መንግሥታዊም አይደለም፡፡ ለዚህ በርካታ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል።
የወልቃይት ጥያቄ አንዱ ነው፡፡ የወልቃትን ጥያቄ መነሳቱ ሳይሆን የተስተናገደበት መንገድ ነው ችግር የሆነው፡፡ የተስተናገደበት መንገድ እስከ ግጭት አምርቷል፡፡ የራያ ህዝብ ጥያቄ አለ፡፡ እንደ ወልቃይት ጎልቶ በተደራጀ መልኩ ላይመጣ ይችላል፡፡ ግን በተለያየ መልኩ እየተነሳ ነው፡፡ ስለዚህ ግጭት ሳይፈጠር፣ ወደ እርስ በእርስ አለመግባባት ሳያመራ ህዝብን ማነጋገርና ለመፍትሄ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በተለይ የኮንሶ ህዝቦች ጥያቄ ነበር፡፡ እርሱም ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ ተገብቷል። የህዝቦች መፈናቀልና የቤት ቃጠሎ ተከስቷል፡፡ ለምን እዚያ ደረጃ ላይ ይደርሳል? ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
ኦሮሚያ ላይ የዛይ ሕዝቦች ጥያቄ አለ፡፡ ራስን በራስ የማስተዳደርና ማንነትን እንደ አንድ ቡድን፣ እንደ አንድ የህብረተሰብ ክፍል የመቁጠር ሁኔታ ማለት ነው፡፡ እኛ ኦሮሞዎች አይደለንም፤ ዛዮች ነን። የራሳችን ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ አለን ብለው እየጠየቁ ነው፡፡ ግን እስከአሁን መልስ አላገኙም፡፡ ስለዚህ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ቶሎ መልስ መስጠት አለበት፡፡
ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተገቢውን ውክልና እንዲያገኙ መፈቀድ አለበት፡፡ በየክልሉ እንዲህ ዓይነት ጥይቄዎች ስለሚነሱ የፌዴራል መንግሥቱ ይህንን ማበረታታት አለበት፡፡ የአገሪቱ መሪዎች ሳይቀሩ «ይህ የጥቂቶች ጥያቄና ጉዳይ ነው እንጂ የህዝብ አይደለም» ብለው ባገኙት መድረክና አጋጣሚ በድፍረት ይናገራሉ፡፡ ይህንን የሚሉት ግን አስጠንተውና የተሟላ መረጃ ይዘው አይደለም። በመሆኑም ከዚህ መውጣት ይገባል፡፡
ክልሎችም እንደገና መደራጀት አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ በጥናት ላይ ተመስርቶ፣ የህዝቦችን ጥያቄ በሚመልስ መልኩ መሠራት አለበት፡፡ ይሄ ማለት እንደገና ሙሉ ለሙሉ ፈርሰው ይሠሩ ማለት አይደለም፡፡ ትላልቅ ቦታና ብዙ ህዝብ ያለው ክልል አለ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ትንሽ ህዝብና ትንሽ መሬት ያለው ክልል አለ፡፡ ይህንን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ማጣጣም ይገባል፡፡
የመንግሥትን በጀት ባግባቡ ለመጠቀም፣ የተፋጠነ፣ ቅርበት ያለውና ቀልጣፋ አስተዳደር ለመፍጠርና በልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ይጠቅማል፡፡ ለምን ሦስና አራት የኦሮሚያ እና የአማራ ክልሎችን መፍጠር አንችልም? ለምን ሁለት የሶማሌ ክልሎችን መፍጠር አንችልም? በመልክዓምድራዊ የሶማሌ ክልል በጣም ሰፊ ነው፡፡ በህዝብ ቁጥር ብዙ ላይሆን ይችላል፡፡ ግን ከጎዴ እስከ ጅግጅጋ ከተማ ያለውን ስናይ ምናልባትም ከኦሮሚያና ከአማራ በቆዳ ስፋት ሊሰፋ ይችላል፡፡ የደቡብ ክልል አምስት ክልሎች ተጨፍልቀው ነው ወደ አንድ የመጡት፡፡ የፌዴራል ስርዓቱ በደንብ እንዲሠራ ካስፈለገ አምስትና ስድስት የደቡብ ክልሎችን ለምንድን ነው የማንፈጥረው? ምዕራብ ያሉት ሸካና ከፋ አካባቢ ያሉ ዞኖች ወደ ሃዋሳ ለመምጣት ረጅም ኪሎ ሜትሮችን ያቋርጣሉ፡፡ በአዲስ አበባ ዞረው ይሄዳሉ፡፡ መሰረተ ልማታችን የተጠናከረ አይደለም፡፡ ይህ በተሟላ መልኩ ሥራ ላይ እስኪውል ድረስ እንደገና ድንበሮቹን ማስተካከል የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡ ከተስተካከለ የፌዴራል ስርዓት በቋንቋም፣ በመልክዓምድራዊ አቀማመጥም በትክክል ሊያስተናግድ ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ የተገበረችው ፌዴራሊዝም በራሱ ለግጭቶች መንስኤ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡ ባለፈው በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል የተከሰተውን ግጭት ማንሳት ይቻላል እንዲህ ዓይነቱ ነገር የሚመነጨው ከምንድን ነው? መፍትሔውስ ምንድን ነው ይላሉ?
ዶክተር ሲሳይ፦ አሁን በየክልሎቹ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች የፌዴራል ስርዓቱ ያመጣቸው ችግሮች ናቸው ብዬ አላምንም፡፡ የፌዴራል ስርዓቱን የተገበርንበት መንገድ ግን የፈጠረው ችግር አለ፡፡ ስለዚህ ችግሩ አተገባበሩ ላይ ነው። በተለይም በብሄር ብሄረሰብ ወይንም በቋንቋ ላይ በተመሠረተ መልኩ የፌዴራል ስርዓት የሚያራምዱ አገሮች አሉ፡፡ ተደጋግሞ በምሳሌ እንደሚነሳውም ስዊዘርላድ ሃይማኖትና በተወሰነ የቋንቋ መልክ አለው፡፡ የህንድ የባህል፣ የቋንቋና የመሳሰሉት ነገሮች ታሳቢ ተደርገዋል፡፡ ስለዚህ በቋንቋ ላይም ይሁን በመልክዓምድራዊ ላይ ተመስርቶ ሥራ ላይ የሚውለው የፌዴራል መንግሥት ለግጭት መንስኤ ሊሆን አይችልም፡፡
በእርግጥ ታፍኖና በተለያየ መልኩ መብቱን አጥቶ የኖረ ህዝብ በአንድ ጊዜ ሁሉም መብቱ ሲሰጠው የሚፈጠር ነገር አለ፡፡ አንድ ቀላል ምሳሌ ላንሳ እምቦሳ እያደገ ሲሄድ ጥጃ ሊባል ይችላል፡፡ መጀመሪያ እምቦሳው እንዳይጠፋ ታስሮ ይቆያል፡፡ በኋላ ላይ ሲለቀቅ በስርዓቱ ካልተያዘ በስተቀር ይፈነጥዛል፣ በጣም ይሮጣል። ስለዚህ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል፡፡ በመሆኑም ከመለቀቁ በፊት መሄድ መለማመድ አለበት፡፡ በኢትዮጵያም ፌዴራልና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በአንድ ጊዜ ተግባራዊ አደረግን፡፡ ዘመናዊ የፌዴራል ስርዓት አዲስ ነው፡፡ አዲስ ነገር ደግሞ ወደ ተግባር ሲመጣ የራሱ ችግሮች አሉት፡፡
ሁለተኛው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለአገሪቱ አዲስ ነው፡፡ ፌዴራሊዝምና ዴሞክራሲ ሁለት ትላልቅ ነገሮች በአንድ ላይ ተግባር ላይ ሲውሉ መደነቃቀፍ ያለ ነው፡፡ ሌላው ትልቁ ችግር ለብሄረሰባዊ፣ ለአካባቢያዊ ማንነት ትልቅ ቦታ ተሰጠ፡፡ ኢትዮጵያዊነትና አካባቢያዊነት ሚዛኑን ጠብቆ እንዲሄድ አልተደረገም፡፡
በተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ ራሳቸው የማድላት አጠቃላይ አገራዊ ማንነትን ያለማየት ችግሮች ነበሩ፡፡ በዚህ ምክንያት በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ከ700 ሺ በላይ ህዝብ የተፈናቀለበት፤ በትግራይና በአማራም ይነስም ይብዛም ወደ ግጭት ባያመራም ጥያቄዎች ጎልተው ይነሱ የነበሩበት፣ ለረጅም ጊዜም ሳይመለስ የቆየበት ሁኔታ ነበር፡፡ እርሱን ተከትሎ ደግሞ የወልቃይት፣ የቅማንት ጥያቄዎች እንደነበሩ እናስታውሳለን፡፡ የቅማንት ጉዳይ በወቅቱ ምላሽ ባለማግኘቱ ወደ ግጭት አምርቶ ነበር፡፡ በሌሎችም ያሉ ችግሮች እነዚህ ናቸው፡፡
ግጭቶች በፊትም ነበሩ ፤አሁን ጎልቶ የወጣው የማህበራዊ ሚዲያውና የመገናኛ ብዙሃን አጉልተው ስለዘገቡትና ስላራገቡት ነው። ነገር ግን ድሮም ጀምሮ በግጦሽ፣ በውሃ፣ በባህል አለመጣጣም ላይ የተመሰረቱ ግጭቶች ነበሩ፡፡ ጎልተው ግን በብሄር ብሄረሰቦች መካከል ተብሎ ተነስቶ አያውቅም፡፡ ምክንያቱም ማዕከላዊ መንግሥቱ ጠንካራ በመሆኑና በሚዲያ የማይወጣበት ሁኔታም ስለነበረ ብዙ ጎልተው አይነሱም ነበር፡፡ ግጭቶች ወደፊትም ይኖራሉ፡፡ ቶሎ መፍትሔ ከተሰጣቸው አንዳንድ ጊዜ ግጭቶች መልካም ነገር አላቸው፡፡
አዲስ ዘመን፦የተሳሰረ ማንነትን መፍጠር አስፈላጊ መሆኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች ይነሳል። ይህንን እንዴት መፍጠር ይቻላል?
ዶክተር ሲሳይ፦ የተሳሰረ ማንነት ለመፍጠር ኢትዮጵያዊነት ላይ መሥራት ይጠይቃል፡፡ ትልቁ ችግር በሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ በተለይም በታሪክ ላይ እየተሠራ አለመሆኑ ነው፡፡ የታሪክ ትምህርት አሁን አይሰጥም፡፡ በፊት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ኢኮኖሚና ጂኦግራፊ ትምህርቶች ይሰጡ ነበር፡፡ አሁን የለም፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችም የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ባለመማራቸው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለው ተማሪ ታሪክን የማያውቅ ነው፡፡
ሁለተኛው የቋንቋ ጉዳይ ነው፡፡ ቋንቋ ለመግባባት በጣም ወሳኝ ቢሆንም የሚያግባባንን እየያዝን አይደለም፡፡ ሊያግባባ የሚችል የጋራ ቋንቋ ሊኖር ሲገባ አሁን የሚያግባባን ቋንቋ አልተያዘም፡፡ አማርኛ ቋንቋ የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ተብሏል አራት የሚሆኑ ክልሎችም ይጠቀሙበታል፤ ነገር ግን በሚገባው ደረጃ በሚያግባባ መልኩ እየተሠራበት አይደለም፡፡ ከአንዳንድ ክልሎች የሚመጡ ተማሪዎች ከፍተኛ ትምህርት ላይ በጣም ያስቸግራሉ፡፡ ወይ እንግሊዝኛን አልያም አማርኛን ባግባቡ ችለው አይመጡም፡፡ በየትኛው አንግባባ የሚለው አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህ ቀላሉ ምሳሌ ነው፡፡ ሁሉም ክልሎች
ፌዴራል ላይ የተሟላ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ካስፈለገ የፌዴራሉን ቋንቋ መቻል አለባቸው፡፡ ተጨማሪ ቋንቋ ቢኖርም ጠቃሚ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንደመጫን አድርጎ የማየት ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ ካናዳ አንድ ክልል ብቻ ነው የፈረንሳይኛ ተናጋሪ ክልል ያለው ኪዩቤክ ግዛት የሚባለው ነው፡፡ ይሄ የፌዴራሉም የሥራ ቋንቋ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥም ለምሳሌ ብዙ ህዝብ ያለበትን ብሄረሰብ በቁጥር ወስዶ ተጨማሪ ቋንቋ ቢኖር ምን ችግር አለው? ይህንን ታሳቢ ማድረግ ይቻላል፡፡
ከዚህም በላይ ሌሎች ወደ አንድነት የሚያመጡ፣ የሚያስተሳስሩና የሚያግባቡ ማህበራዊ እሴቶችን ማጠናከር ይገባል፡፡ ከዚህ በፊት ያሉ ሀብቶች፣ ማህበራዊ እሴቶች አሉ። እነዚህን የሚያጠናክሩ ማንነትን ጠብቆ አጣጥሞ መሄድ የሚቻልበት ሁኔታ አለ፡፡ በዚህ ረገድ ባለፉት 26 ዓመታት ጉልህ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያንን አንድ የሚያደርገን የጋራ ድልና ታሪካችን አንዱ ነው፡፡ ለምሳሌ ዓድዋ በዓልን እናንሳ በትክክል እየተከበረ አይደለም፡፡ የብሄር ብሄረሰብ በዓልን ወይንም የፓርቲ ምስረታ በዓልን የሚያክል የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን፣ የገንዘብ በጀት ይሰጠው ነበር ወይ? ብለን ብንመለከት የምንታዘበው ነው፡፡ ስለዚህ የጋራ የሚያደርጉ በዓሎችን ዋጋ በመስጠት በደንብ ማክበር ተገቢ ነው፡፡ ከዚያም የቀዘቀዘውና የደከመውን አንድነት ወደ ትክክለኛው ቦታ ማምጣት ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን፦ ህገ መንግሥቱ ላይ ከአንድ ክልል ወደ ሌሎች ክልሎች በመዘዋወር ማልማት እንደሚቻል ተቀምጧል፡፡ አንዳንድ ክልሎች ይህ መብት እንዳይተገበር ተጽእኖ ሲፈጥሩ ይስተዋላል። እነዚህ ሁለት ሃሳቦች ከህገ መንግሥቱ ጋር አይጣረሱም?
ዶክተር ሲሳይ፦ እውነት ነው፤ በተግባር ያለው ነገር ከህገ መንግሥቱ ጋር ይጣረሳል፡፡ በተግባር ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ የክልል መንግሥታትም ከፌዴራል ህገ መንግሥት ጋር ይጣረሳሉ፡፡ ይህንን አይቶ በደንብ ማረም ያለበት የፌዴራል መንግሥት ነው፡፡ ምክንያቱም ህገ መንግሥት የአገሪቱ የበላይ ህግ ነውና፡፡ የክልሎች ህገ መንግሥትም ሆነ ሌሎች ህጎች ትግበራቸው ከዚያ በታች ነው፡፡ ህገ መንግሥቱን የሚጻረሩ ከሆነ ውድቅ መደረግ አለበት፡፡ ይህንን የማስከበር ጉዳይ የፌዴራል መንግሥት ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ዜጎች ወደ ፈለጉት አካባቢ ሄደው መሥራትም፣ መኖርም ይችላሉ፡፡ ይህ የእነርሱ ምርጫ እንጂ የመንግሥት ወይንም የክልሎች ኃላፊነት ወይም ስልጣን አይደለም፡፡ ሆኖም ግን አሁን አንድ ሰው ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል ሲሄድ ሃገሩ ላይ የኖረ ሳይሆን ወደ ሌላ አገር የሄደ ያህል የሚቆጥርበት ስሜትና ስጋት ውስጥ የሚወድቅበት ሁኔታ ይታያል፡፡ ይህ ህገ መንግሥታዊም ህጋዊም ባለመሆኑ መታረም አለበት፡፡
ትልቁ ችግር ከአንድ ጽንፍ ወደ ሌላው ጽንፍ የመሄድ ችግር ነው፡፡ ቀደም ሲል ለኢትዮጵያ አንድነት ትልቅ ቦታ ተሰጠና ከጫፍ እስከ ጫፍ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ነው ማውራት ያለብህ የሚል ነበር፡፡ ስለራሱ ማንነት፣ ስለአካባቢያዊ አስተዳደር ብዙ መብት የሚፈቅድ አልነበረም፡፡ አሁን ደግሞ ከኢትዮጵያዊነት የተማከለ አሠራር በጣም የተለጠጠና ያልተማከለ አሠራር ተገለበጠና ክልሎች ራሳችሁን በራሳችሁ ታስተዳድራላችሁ ሲባሉ ያን ክልል ለራስ አድርጎ ብቻ የመውሰድ ነገር ታየ፡፡ ይሄ እንደ ችግር የሆነው አስተምህሮት ላይ በደንብ ባለመሠራቱ ነው፡፡ የጋራ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ አልተተገበረም፡፡ ክልሎችም ህጉን አክብረው እንዲሄዱ፣ ሁሉንም ታሳቢ አድርገው እንዲሠሩ የሚያደርግ ሥራ አልተሠራም፡፡ እነዚህ የፈጠሯቸው እንጂ በህገ መንግሥቱ መሰረት በነፃ የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራት ጉዳይ በዜጎች ምርጫ የሚወሰን እንጂ ክልሎች ወይንም የፌዴራል መንግሥቱ ምርጫ አይደሉም፡፡
አዲስ ዘመን፦ ክልሎች ክልላዊ መንግሥት ተብለው የሚጠሩት የመንግሥት ሥልጣን ስለሚተገብሩ ነው ወይስ ሌላ ምክንያት አለው?
ዶክተር ሲሳይ፦ መንግሥት ሲባል ብዙ ጊዜ ማዕከላዊ መንግሥትን አድርገን ነው የምንረዳው፡፡ ነገርግን ቀበሌም መንግሥት ነው፡፡ የአካባቢ አስተዳደር አለ፡፡ ወደ ፌዴራል ስንመጣ መንግሥት ነው፡፡ ክልሎችም መንግሥት ሊባሉ ይችላሉ ችግር የለውም፡፡ ክልል ላይ መንግሥት አለ፣ ወረዳ ላይ መንግሥት ይኖራል፣ በተመሳሳይ ቀበሌ ውስጥም መንግሥት አለ፡፡ ዞሮ ዞሮ ለእነዚህ ደረጃዎችና እርከኖች በህገ መንግሥቱ መሰረት የተመጠነ ሥልጣን ይሰጣል፡፡
ህገ መንግሥቱ ለፌዴራሉና ለክልል መንግሥታት የሚሰጠው ሥልጣን አለ፣ የክልል ህገ መንግሥታት ደግሞ ለክልሉ፣ ለዞንና ለወረዳ የሚሰጡት ሥልጣንና ተግባር አለ፡፡ ይህ ታሳቢ ተደርጎ ይሠራል። ዋናው ነገር በእነዚህ መንግሥታት መካከል ያለውን ግንኙነት ተቋማዊ የማድረግ ጉዳይ ነው፡፡ ይሄ በስርዓትና በህግ የሚመራ መሆን አለበት፡፡ በአገራችን ያለው አንዱ ችግር በህግና በስርዓት አለመመራት፤ሥራው ብዙ ጊዜ ሲተገበር የሚታየውም በፓርቲ መዋቅር ነው፡፡ በግንባሩ አባላት መካከል ስምምነት ከተደረሰ ወደ ሥራ የሚገባበት ሁኔታ አለ፡፡ ትልቁ ስህተት ይህ ይመስለኛል፡፡
ባለፈው ሰሞን የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ የማዕከላዊ ምርመራ እንዲዘጋ ወስኗል፡፡ ይህንን ዜና የመገናኛ ብዙሃን እንኳን የዘገባችሁት ‹‹የማዕከላዊ ምርመራ እንዲዘጋ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ በወሰነው መሰረት ተዘጋ›› ብላችሁ ነው፡፡ እኔ እንዲህ ዓይነት ስህተት ስመለከት አዝናለሁ፡፡ ይሄ ስህተት በምንም ዓይነት መልኩ ተቀባይነት የለውም፡፡
የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎችን እንደ ፓርቲ ሊወስን ይችላል፡፡ ይሄ ውሳኔ ወደ መንግሥት ሄዶ የመንግሥት አካላት ከወሰኑ በኋላ ነው ህጋዊ ሥራዎች የሚፈጸሙት፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ይወስን አይወስን የመገናኛ ብዙሃን ጉዳዩ መሆን አልነበረበትም፡፡ የፌዴራል መንግሥት በወሰነው መሰረት ተዘጋ፣ የፌዴራል መንግሥት በወሰነው መሰረት እስረኞች ተለቀቁ ሲባል አይሰማም፡፡ በፓርቲ ያሉ ሥራዎች ስለሚጎሉ መደበላለቅ ያለ ይመስለኛል፡፡ ይህ መስተካከልና መታረም አለበት፡፡ መንግሥት የሚለው ስያሜ ችግር የለውም፤ በዚያው ልክ ሥልጣንና ተግባር ስላለው፣ የመንግሥት ኃላፊነትን ስለሚረከብ የክልል መንግሥታት እያልን እንጠራለን፡፡
አዲስ ዘመን፦ ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ሲሳይ፦ እኔም አመሰግናለሁ።

ዘላለም ግዛው

Published in ፖለቲካ

ኮንስትራክሽን የማይዳስሰው ዘርፍ የለም፡፡ የትምህርት፣ የጤና፣ የውሃ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የመብራት፣ የኢንዱስትሪ፣ሌሎች... ተቋማትን ልናነሳ እንችላለን፡፡ ዘርፎቹን ለማስፋፋት አስተዋጽኦው አስፈላጊ በመሆኑ የሚመደበው በጀትም ከፍተኛ መጠን ያለው ነው፡፡ ተዋናዮቹም በርካቶች በመሆናቸው ለሙስናና ብልሹ አሰራሮች ተጋላጭነቱ ሰፊ ነው፡፡
የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ የዓለም አገራት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ግዙፍነት፣ ውስብስብ ባህሪ፣ ከፕሮጀክቶች አፈጻጸም፣ የተራዘመ የፍቃድ አሰጣጥ ሂደት፣ ከሚያሳትፋቸው በርካታ የስራ ተቋራጮች አንጻር ከፍተኛ ሙስናና ብልሹ አሰራር ይፈጸማል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ መንግስታት ለኮንስትራክሽን ዘርፍ ከሚመድቡት በጀት እስከ 30 በመቶ ያህሉ በሙስና ሊባክን እንደሚችልም የተሰሩ ጥናቶች ያመለክታሉ ።
የፌዴራል ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ አጦ እንዳሉት የኮንስትራክሽን ዘርፉን የሙስና ተጋላጭነት ስፋት በመገንዘብ ኮሚሽኑ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ሙስናንና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል እንዲሁም መልካም ስነ ምግባርን ለማስፋፋት ከተለያዩ አካላትና ማህበራት ጋር ቅንጅት ፈጥሮ እየሰራ ነው፡፡
ለዘርፉ የሚመደበው መዋዕለ ንዋይ በሙሰኞች ከተመዘበረ ግንባታዎቹ የማያስተማምኑ፣ አደገኝነታቸው የሰፋና ዋጋቸው እጅግ የተጋነነ ይሆናሉ። የዚህ ድምር ውጤትም ለህይወት መጥፋትና ለከፋ የኢኮኖሚ ጉዳት በመዳረግ ከድህነት ለመውጣት በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡
በመሆኑም በዘርፉ የተሰማሩ ተሳታፊዎች ተወዳዳሪ ሆነው ለመዝለቅ እንዲችሉ ግልጽነት ያለውና የአፈጻጸም ብቃትን ግምት ውስጥ ያስገባ አካሄድ መከተል አለባቸው ብለዋል።
ለዚህም የዘርፉ ተዋናዩች የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በኮሚሽኑ የሙስና መከላከል ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ሙሉጌታ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የመንግስት ወጪ አብዛኛው በግንባታ ዕቃዎች ግዢ ላይ የሚውል በመሆኑ በግዥ ስርዓቱ ዙሪያ ጥናት ተደርጓል። በጥናቱም ከህጎችና ከአፈጻጸም መመሪያ አኳያ መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዩች እንዳሉም ተለይቷል።
እንዲሁም ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል በኮንስትራክሽን ዘርፉ በተለያዩ ጊዜያቶች ያካሄዳቸው ጥናቶችን ተግባራዊነት ለመከታተል በየስድስት ወራት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ይደረጋል፡፡ በተለይም ካለፉት አንድ አመት ተኩል ወዲህ የተለያዩ ውጫዊና ውስጣዊ ችግሮች መኖር ለቅንጅቱ የተሰጠው ትኩረት እንዲላላ፣ የአተገባበር ደረጃውም እየቀነሰ እንዲሄድ አድርጓል።
የሀብኮን ኮንሰልት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሀጎስ አብዲ፤ በጣም የተጋነነ ወይም በጣም ዝቅ ያለ የማምረቻ ዋጋን የማይሸፍን የጨረታ ዋጋ፣ በግንባታ ሂደት ላይ የሚያጋጥሙ የዲዛይንና ዝርዝር የስራ ለውጦች እንዲሁም በግንባታ ሂደት ላይ የሚያጋጥሙ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ለማስተካከል የሚያስችሉ ጥናቶቹን ከፌዴራል የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ጋር በመተባበር እንዳጠኗቸው ይናገራሉ፡፡ እጅግ በጣም ዝቅ ያለ ወይም እጅግ በጣም የተጋነነ የጨረታ ዋጋ ማቅረብ ትክክል እንዳልሆነም ይናገራሉ፡፡ የጨረታ ዋጋው ከምህንድስና ጋር ተመሳሳይ ሆኖ በውስጡ የተቀመጡ ዝርዝር ስራዎች ከፍ እና ዝቅ ያሉ፣ የተዛቡ፣ የኮንትራት ዋጋዎች ውል ሲፈጸምም የሚያስከትለውን ችግር ጥናቱ ማመልከቱንም ይናገራሉ፡፡
ይሄ አካሄድ ተቋራጩ ስራን መፈጸም የማይችልበት፣ ጥራቱ ዝቅ እንዲል የሚያደርግበት እንዲሁም ሌሎች ተቋራጮች ወደ ስራ እንዳይገቡ የሚያደርግበት ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ የተጋነነ ዋጋ ሲቀርብም የመንግስት ገንዘብ አላግባብ መባከንን የሚያስትል እንደመሆኑ ይነቀፋል፡፡ ወደፊት ስራው ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች ካሉም ላልተፈለገ ወጪ ይዳርጋል፡፡ በመሆኑም እነዚህ ሁኔታዎች መወገድና መስተካከል ይገባቸዋል። ክፍተቶቹን ለማስተካከልም ሆነ ተገቢ ያልሆኑ ልምዶችን ለማስወገድ የህግ ማዕቀፍ ያስፈልጋል ሲሉ ይጠቁማሉ፡፡
ሆኖም ኤጀንሲው የግዢ መመሪያ ማስተካከያ ቁጥር አንድ እና ቁጥር ሁለት ማውጣቱንና የግዢ ባለሙያዎችን የማብቃት ስራ መስራቱን ይናገራሉ። የኮንስትራክሽን ስራው ሙሉ በሙሉ ከእነርሱ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ወደፊትም ዝርዝር መመሪያ እንደሚያስፈልግ መታየት ይገባዋል ብለዋል፡፡
ሌላው የተሰራው ጥናት ከዲዛይንና ከስምምነት መመሪያ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ምክንያቱም ግንባታ ከተጀመረ በኋላ የዲዛይንና ዝርዝር የስምምነት መመሪያ በተደጋጋሚ ጊዜያቶች እንደሚከሰትም ያመለክታሉ፡፡ ግንባታዎች ሲጀመሩ በተያዘበት ዋጋ አያልቁም፤ ምክንያቱ ደግሞ የዲዛይንና ዝርዝር የስምምነት መመሪያዎች ስለሚቀያየሩ ነው ባይ ናቸው፡፡ ሁለተኛው ጥናት የሚቀያየሩበትን ምክንያት በማጥናት ችግሮቹን እና የመፍትሄ ሃሳቦች መመላከቱን ነው የሚናገሩት፡፡
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ በጥናቱ ከአማካሪዎች፣ ከአሰሪ መስሪያ ቤቶች ጋር የሚያያዙና አንዳንዴም ያልተጠበቁ ችግሮች የሚያጋጥምበት ሁኔታ አለ፡፡ ከአማካሪው ጋር የሚገናኘው ባለሙያው የሚያቀርበው የዲዛይን ስራ ያልተሟላ፣ የተሳሳተ፣ አልያም የባለቤቱን ፍላጎት ሙሉ ለሙሉ ያላማከለ ነው፡፡ በተጨማሪም መንግስት ያወጣቸውን አስገዳጅ መመሪያና ኮዶቹን ያልተከተለ ሆኖ ይገኛል፡፡
ስለዚህ አማካሪዎች እነዚህን ሁኔታዎች ባሟላ ሁኔታ የራሳቸውን ዝርዝር የውስጥ መመሪያና የጥራት ቁጥጥር ክፍል ፈጥረው ሊሰሩ ይገባል፡፡ ይሄ ስራ ለአማካሪዎች የሚተው ከሆነ፣ ክትትልና አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ አሁንም አይተገበርም ሲሉ ኢንጂነር ሀጎስ ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ አማካሪዎች ሲመዘገቡ በቂ የሰው ሃይል እንዳላቸውና አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላታቸው መታየት ይገባዋል፡፡ አሁን ያለው ለአማካሪዎች ደረጃ የሚሰጥበት የምዝገባ ስርዓት በአብዛኛው በቁስ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የዲዛይንና የስምምነት መመሪያ ችግሮችን የሚፈታ ባለመሆኑ መቀየር እንዳለበት ይናገራሉ፡፡
በዲዛይን ስራ አመራር ስህተት ያለባቸውንና የባለቤትን ፍላጎት ያለማሟላት ችግሮችን ሊቀርፍ የሚችል የአሰራር ስልት መቀየሱ መታየት ይገባዋል የሚሉት የጥናቱ አቅራቢ፤ ባለሙያዎች ብቁ ለመባል አምስት አመታት መስራት ብቻ ሳይሆን ዕውቀታቸውና አተገባበራቸው ምን እንደሚመስል፣ ከሰዎች ጋር ያላቸው ተግባቦትና የሰራተኞች አስተዳደር አቅማቸው እየተገመገመ ደረጃ ሊሰጣቸው ይገባል ሲሉም ያክላሉ፡፡
ለምሳሌ በተሰጠው ዋጋና ጥራት፣ በወቅቱ መጨረስ ለእያንዳንዱ አማካሪ የመገምገሚያ መስፈርት ተደርጎ በየዓመቱ መመዘን ይገባል፡፡ ይህ ሂደት ወደፊት ጥሩ ስራ ለመስራት ለሚፈልጉ አሰሪዎች ባለሙያ ለማግኘት ተጨባጭ ማስረጃ እንዲያገኙ ያስችላል፡፡ ለዚህ የእያንዳንዱን አካል አፈጻጸም እየለካ በተጨባጭ ማስረጃ የሚመዘግብ አካል ሊኖር ይገባል፡፡
እያንዳንዱ አሰሪ መስሪያ ቤትም ይህንን እንዲፈጽም አስገዳጅ ህግ ሊኖር እንደሚገባ ኢንጂነር ሀጎስ ይናገራሉ፡፡ የህግ ማዕቀፍ ከወጣ አሰሪዎች አፈጻጸምን ለክተው ለሚመለከተው አካል ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ የባለሙያዎቹን ብቃት፣ የምዝገባ ስርዓቱ መሻሻል፤ አመላካች የትግበራ መለኪያዎች በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲኖር ማድረግ እንደሚያስፈልግ በጥናቱ ተገልጿል።
የምዝገባ ስርዓቱን በማስተካከል፣ የህግ ማዕቀፍ እና ዝርዝር መመሪያ በማዘጋጀት፣ የባለሙያዎቹን ብቃት መዝኖ ደረጃ በመስጠት ዙሪያ የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ፣ የኮንስትራክሽን ሚኒስትር፣ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ትኩረት ተሰጥቶት እንዲተገበር በማድረግና የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው ገልጸዋል፡፡
በመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የኦዲትና ክትትል ዳይሬክተር ወይዘሮ መቅደስ ብርሃኑ፤ አብዛኛው የመንግስት ወጪ በግንባታ ዕቃዎች ግዢ የሚውል መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ የግንባታ ዕቃ ግዢ ለሙስና ተጋላጭ በመሆኑ ከህጎችና ከአፈጻጸም መመሪያ አንጻር መሻሻል በሚኖርባቸው ጉዳዩች ላይ የፌዴራል የስነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን የሚያደርጋቸው ጥናቶች ማሻሻያ ለማድረግ ጠቃሚ ግብዓት ተደርገው የሚወሰዱ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
በተለይም የግንባታ ዕቃ ግዢ ለአገር ከሚያበረከረተው አስተዋጽኦ አንጻር ከፍተኛ ድርሻ ያለው በመሆኑ ተጋላጭነቱን ለመቀነስ ቀደም ሲልም የህግ ማሻሻያዎች ተሰርተዋል ሲሉ ወይዘሮ መቅደስ ያስታውሳሉ፡፡ በ2008 ዓ.ም ከግንባታ ግዢ ጋር በተያያዘ የተደረገውን ለውጥ በግብአትነት ይጠቁማሉ፡፡ በቀጣይም ግልጽ አሰራር ለመፍጠር የህግ ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ ያመለክታሉ፡፡
የአማካሪ መሃንዲሶች፣ የምህንድስና ግምት ዋጋ መብለጥና ማነስ፣ ያልተመጣጠነ የጨረታ ዋጋ በመቅረቡ ምክንያት የማስተካከያ እርምጃዎች ይወስዳል፡፡ ኤጀንሲው ተቆጣጣሪ አካል እንደመሆኑ የወጡ አዋጆችና የአፈጻጸም መመሪያዎችን በመከተል ባለድርሻዎች መፈጸማቸውን የመቆጣጠር ሃላፊነት አለበት፡፡
በመሆኑም ይላሉ ወይዘሮ መቅደስ በጥናት የተጠቆሙ ሃሳቦች ላይ የህግ ማሻሻያ ለማድረግ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ቀደም ሲል በአዋጁ 649/2000 የወጣውን አዋጅ ለማሻሻል ረቂቁ ተዘጋጅቶ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ቀርቧል፡፡ አዋጁን ተከትሎ የአፈጻጸም መመሪያ ይዘጋጃል፣ መደበኛ የጨረታ ሰነዶች ዝግጅት ላይ የማስተካከያ ስራዎች ይተገበራሉ ብለዋል፡፡
ከግንባታ ግዢ ጋር በተያያዘ ለውጥ መደረጉን የጠቆሙት ሃላፊዋ፤ አዋጁ ከግንባታ ግዢ ፣ ከዋጋ መለዋወጥ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ችግር ይቀርፋል፤ ተጫራቾችን ለመምረጥ መደበኛ የጨረታ ሰነዶች ማሟላት ያለባቸው መስፈርቶችና ሌሎች በምክረ ሃሳብ የተጠቆሙት ይዳሰሳሉ ብለዋል፡፡

ዘላለም ግዛው  

Published in ኢኮኖሚ

በእርስበርስ ግጭት በርካታ ዜጎቿ ለስደት እየተዳረጉ የሚገኙባት መካከለኛ አፍሪካዊት አገር ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከገባችበት ፖለቲካዊ ቀውስ ሳትወጣ ሌላ ፈተና ተጋርጦባታል። «በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ» እንደሚባለውም ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የምዕራብ አፍሪካ አገራት ዜጎችን ሕይወት ሲቀጥፍ የነበረው የኢቦላ ቫይረስ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ሰሞኑን እንደጎበኛት እየተነገረ ነው።
ከቀናት በፊት በአገሪቱ በተደረገ ድንገተኛ የጤና ምርመራ ሃያ አንድ ሰዎች በቫይረሱ ሳይጠቁ እንዳልቀረም የአልጄዚራ ዘገባ ጠቁሟል። በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሰሜን ምዕራባዊ ክፍል ቫይረሱ ዳግም እንዳገረሸ የጤና ባለሙያዎች ያረጋገጡ ሲሆን፣ የአስራ ሰባት ሰዎች ሕይወት በቫይረስ ሳቢያ እንዳለፈም ዘገባው አመልክቷል።
የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ባለፈው ማክሰኞ እንዳመለከተው፣ ቢኮሮ ከተባለችው ከተማ አቅራቢያ ኢኮኮ ኢምፔንጌ በተባለው ስፍራ የቫይረሱ ምልክት ታይቶባቸው የላቦራቶሪ ምርመራ ከተደረገላቸው ሃያ አንድ ሰዎች መካከል ሁለቱ በቫይረሱ እንደተጠቁ ተረጋግጧል። በኢኩዌተር አውራጃም በቫይረሱ ተጠቅተዋል ተብለው ከተጠረጠሩ ሰዎች የአምስት ያህሉ የደም ናሙና ወደ መዲናዋ ኪንሻሳ ተወስዶ ምርመራ እየተደረገበት እንደሚገኝ የአገሪቱ የጤና ኃላፊዎች ገልጸዋል።
የኢቦላ ቫይረስ ዳግም እንዳገረሸ በተነገረው ስፍራ ባለፉት አምስት ሳምንታት የአስራ ሰባት ሰዎች ሕይወት እንዳለፈ የተገለጸ ሲሆን የእነዚህ ሰዎች ህልፈተ ሕይወት ግን ከቫይረሱ ጋር የተያያዘ ሆኖ አልተገለጸም ነበር። አሁን ግን የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ቫይረሱ በአገሪቱ መከሰቱን በማረጋገጥ የዓለም አቀፍ እርዳታ ጥሪውን አስተላልፏል። «አገራችን ዳግም በኢቦላ ቫይረስ ተጠቅታለች፤ ከዓለም አቀፉ የጤና ማህበረሰብም አፋጣኝ እርዳታ እንፈልጋለን» በማለት የጤና ሚኒስቴሩ ማሳወቁን አልጄዚራ ዘግቦታል።
ቫይረሱ ከመስፋፋቱ በፊት ለመቆጣጠር ያስችል ዘንድ የሰለጠነ የጤና ባለሙያ እርዳታ እንደሚያስፈልግ የተገለጸ ሲሆን የዓለም የጤና ድርጅትም በጉዳዩ ዙሪያ በትዊተር ገጽ ምላሽ ሰጥቷል። በዚህም ኪንሻሳ በተደረገ የናሙና ምርመራ ከአምስት ሰዎች ሁለቱ በቫይረሱ መጠቃታቸውን ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ማረጋገጫ እንደደረሰው የዓለም የጤና ድርጅት ገልጿል። የዓለም የጤና ድርጅት ሐኪሞች ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የረድኤት የጤና ባለሙያዎችና ከአገሪቱ የጤና ኃላፊዎች ጋር በመሆን ወደ ስፍራው በማምራት ቫይረሱን ለመቆጣጠር እየሰሩ መሆኑም ታውቋል።
የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው በቫይረሱ ከተጠቁ ሰዎች መካከል በአማካኝ ሃምሳ በመቶው ለሞት ይዳረጋሉ። የኢቦላ ቫይረስ በምዕራብ አፍሪካ አገራት ጊኒ፤ ሴራሊዮንና ላይቤሪያ ከተከሰተበት እአአ ከ2013 እስከ 2016 ብቻ ለአስራ አንድ ሺ ሦስት መቶ ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። አሁን ላይ እነዚህ አገራት ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ስማቸው ሲነሳ አይታይም። የመካከለኛዋ አፍሪካዊት አገር ዜጎች ለከፍተኛ የሰብዓዊ ድጋፍ በተጋለጡበትና አሳሳቢ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ በገቡበት ወቅት ከሰው ወደ ሰው በትንሽ ንኪኪ በመተላለፍ ለሞት የሚያበቃው መድኃኒት የለሽ ቫይረስ ኢቦላ መከሰቱ በርካቶችን ያስደነገጠ ነው።
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ በሥልጣን የመቆየት ፍላጎታቸውን ካሳወቁ ወዲህ በአገሪቱ በተፈጠረው ከፍተኛ ቀውስ አስራ ሦስት ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚፈልጉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከወር በፊት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ይህ ቁጥር ዴሞክራቲክ ኮንጎን አስከፊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የምትገኘውን የመካከለኛው ምሥራቅ አገር ሶሪያን በመብለጥ ጭምር ቀዳሚዋ ድጋፍ የምትሻ አገር አድርጓታል። ሰባት ዓመታትን ያስቆጠረው የሶሪያ ቀውስ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ዜጎች ሕይወት ቀጥፎ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች እርዳታ እንዲሹ አድርጓል። ይህም በአፍሪካ አሳሳቢ ቀውስ ውስጥ ከምትገኘው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በእጥፍ ያነሰ ነው።
በመካከለኛው አፍሪካ በተፈጠረው አመፅ ምክንያት አራት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑ ሕፃናት ለሰብዓዊ እርዳታ ተጋልጠዋል። በሌሎች አገራት ቀውስ ምክንያት ትኩረት የተነፈገው የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አሳሳቢ ችግር ለረጅም ዓመታት ስር የሰደደና አሁን ላይ በአሳዛኝ ሁኔታ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛን ለመመልከት ያበቃ ነው። በ2016 ይቋጭ የነበረው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ የሥልጣን ዘመን ሆን ተብሎ እስከ 2018 መራዘሙ ያመጣው መዘዝ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሞት ዕጣ ፈንታ ሲሆን፤ አስራ ሦስት ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ በአስቸኳይ የሚበሉትና የሚጠጡትን ከሌላ ወገን እንዲማፀኑ አድርጓል። ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለእንደዚህ ዓይነት ግጭት አዲስ ባትሆንም የአገሪቱ መንግሥትም ይሁን ሕዝቡ ካለፈው መማር ተስኖት አሁንም የሰቆቃ ኑሮ ይገፋል። እአአ ከ1998 እስከ 2003 በአገሪቱ በተከሰተ ግጭት ከአስር ሺ በላይ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ለሕዝብ ሕይወት ዋጋ የሚሰጥ መንግሥት በመጥፋቱም አምስት ዓመት ሙሉ አገሪቱ አስከፊ ጊዜ ልታሳልፍ እንደቻለች አልጄዚራ በዘገባው አስታውሷል።
ሔማ እና ሌንዱ በተባሉ ጎሳዎች መካከል እአአ በ1970ዎቹ በተከሰተው ግጭት አገሪቱ ሌላ የማይሽር ጠባሳ እንደገጠማት የሚታወስ ሲሆን፣ በእርስበርስ ግጭቱ አገሪቱ ከፍተኛ ድርቅ አጋጥሟት ነበር። ይህን ታሪክ ለመሻር በአገሪቱ መንግሥት በኩል አሁንም ፍላጎት ካለመኖሩ በተጨማሪ ወደ ፊትም ይህ ታሪክ ስለመቀየሩ አጠራጣሪ ደረጃ ላይ ደርሷል።
ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ወደ ኡጋንዳና ቡሩንዲ የእርስ በርስ ግጭትን ሸሽተው የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል። በርካቶች ከዚህች አገር መሰደድ ብቻም ሳይሆን አሰቃቂ ሞት እየደረሰባቸው ይገኛሉ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ እንደገለጸው ከአራት ሳምንታት በፊት ብቻ ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ወደ ዩጋንዳ በጀልባ የገቡ ስደተኞች ቁጥር አንድ ሺ ሦስት መቶ ነበር። እነዚህ ስተደኞች ዩጋንዳ ሲደርሱ ለመቀበል ጊዜያዊ የስደተኛ መቀበያ ካምፕ ቢቋቋምም የውሃ፣ ምግብ፣ መድኃኒትና መጠለያ እጥረት ሁኔታውን እንዳባባሰው ይታወሳል።
በአጠቃላይ ሦስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሕዝብ በተፈጠረው አለመረጋጋት መኖሪያውን ጥሎ የተሰደደ ሲሆን፣ ከሦስት መቶ ሺ የሚበልጡት ስደተኞች አስራ አንድ የአፍሪካ አገራትን እንዳዳረሱም በጥናት ተረጋግጧል። በዚህ ወቅት አጠቃላይ የተራበውን የአገሪቱን ሕዝብ ለመመገብ ሦስት ከመቶ ብቻ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ እንደተገኘ ከወር በፊት የወጡ ዘገባዎችና ሪፖርቶች ያመለክታሉ። በዚህ ላይ በቅርቡ የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ ካጋጠመው የበጀት እጥረት ጋር ተደምሮ ሌላ ቀውስ በአገሪቱ እንደፈጠረም ይታወቃል።
ያጋጠመውን የመድኃኒት፤ የምግብና የመጠጥ ውሃ እጥረት ለመቅረፍ አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከረድኤት ተቋማት መገኘት እንዳለበት ያስታወሰው ዘገባው፣ በአሁኑ ወቅት ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በዓለም ቁጥር አንድ ሰብዓዊ ድጋፍ የምትሻ አገር መሆኗን ያስቀምጣል።
በካምፓላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በቅርቡ ባደረገው ሪፖርት መሠረት ከሃያ ሁለት ሺ የሚበልጡ ስደተኞች ያለውን ግጭት ሸሽተው ወደ ዩጋንዳ ገብተዋል። ከወር በፊት በሦስት ቀናት ጊዜ ውስጥ ብቻ አልበርት ሐይቅን የተሻገሩ የአገሪቱ ዜጎች ቁጥር ሃያ ሁለት ሺ ደርሶ እንደነበርም ይታወሳል። ይህም በያዝነው የፈረንጆች ዓመት መጀመሪያ ብቻ የስደተኞቹን ቁጥር ወደ ሰላሳ አራት ሺ ከፍ ያደርገዋል።
አባታቸው ሎውረንት ካቢላ እኤአ 2001 ላይ መገደላቸውን ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጡት ጆሴፍ ካቢላ 2006 ላይ በምርጫ ፕሬዚዳንት መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ብዙ ያነጋገረውን የ2011 ምርጫም «አሸንፌያለሁ» ብለው ስልጣናቸውን ማራዘማቸው አይዘነጋም። ለጆሴፍ ካቢላ ሁለተኛ ዙርና የመጨረሻ የስልጣን ቆይታ የሚጠናቀቀው እኤአ 2016 ታህሳስ ወር ላይ የነበረ ቢሆንም ምርጫው በተለያዩ ሰበቦች ታጅቦ ሲጓተት ይስተዋላል። ይህን ተከትሎም መንግስትና ተቃዋሚ ቡድኖች ባደረጉት ድርድር ካቢላ እስከ 2017 መጨረሻ ይቆዩ ቢባልም ለተጨማሪ ቀነ ቀጠሮ መራዘሙ አልቀረም። እነዚህ የተስፋና የግጭት ጊዜያት መፍትሄ የሚያገኙበት ወይንም ነገሮች በከፋ መልኩ የሚበላሹበት ይሆናል ቢባልም በፈረንጆቹ ታህሳስ 23 ላይ አርባ ሦስት ሚሊየን ያህል ተመዝጋቢዎች ወደ ምርጫ ጣቢያ እንደሚሄዱ ተጠቁሟል። ይህ በቃል ደረጃ የተቀመጠ ቢሆንም ምርጫውን ለማዘመን በሚል ምክንያት የኤሌክትሮኒክስ ምርጫ ስርዓት ተዘርግቷል መባሉ ነገሩ ሌላ ጥርጣሬ እንዲነሳበት አድርጓል።

ቦጋለ አበበ

Published in ዓለም አቀፍ

አሁን ያለውን ፌዴራላዊ ሥርዓትና ኢህአዴግን የሚቃወሙ አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች ለተቃውሟቸው የሚያቀርቡት ቀዳሚ ምክንያት «አገሪቱን በብሔር፣ በዘር፣ በጎሳ ከፋፈለ» የሚል ነው። በተለይ አገሪቱ በጎሳ ተከፋፈለች የሚሉት ቡድኖች አሁን ያለውን የብሔር ብዝሃነትን የተቀበለን ፌዴራላዊ ሥርዓት አዋርደው ማየት የሚፈልጉ ናቸው። ጎሳ በአንድ ብሔር ወይም ብሔረሰብ ውስጥ ጥብቅ የደም ትስስር ያላቸውን ቤተሰቦች የያዘ አነስተኛ የህብረተሰብ ክፍል ነው። ለምሳሌ በኦሮሞ ውስጥ በርካታ ትላልቅና ንኡስ ጎሳዎች አሉ። ቱለማ፣ ሜጫ፣ ቦረና ባሬንቱ ትላልቅ ጎሳዎች ሲሆኑ በእነዚህ ስር በርካታ ንኡስ ጎሳዎች ደግሞ አሉ። እንደብሔር ግን ሁሉም ኦሮሞዎች ናቸው። አሁን በአገሪቱ የተገነባው ሥርዓት ጎሳን ሳይሆን ብሔርን ወይም ብሔረሰብን መሰረት ያደረገ ሆኖ ሳለ በጎሳ የተከፋፈለ አድርጎ ማቅረብ ግን ስህተት ነው። ያም ሆነ ይህ አሁን ያለውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሥርዓትና ገዢውን ፓርቲ (ኢህአዴግ) ለመቃወም አገሪቱን ከፋፈለ የሚል መቃወሚያ የሚያቀርቡ ቡድኖችን ማንነትና የፌዴራላዊ ሥርዓቱን ፖለቲካዊ መሰረት እንመለከት።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት ወይም ኢህአዴግ አገሪቱን በብሔር አልከፋፈለም። ብሔሮችን ፈጥረው ወይም ከሌላ ቦታ አምጥተው የተከፋፈለች አገርን መመስረት የሚያስችል አቅምም የላቸውም። ኢትዮጵያ የምትባለው ምድር ቀድሞውኑም አንድ ብሔራዊ ማንነት ያላት አገር አይደለችም። ኢትዮጵያ የኦሮሞ፣ ሲዳማ፣ ሱማሌ፣ ወላይታ፣ አፋር፣ ጉራጌ፣ ስልጤ፣ ወዘተ ብሔሮችና ብሔረሰቦች የሚኖሩባት አገር ነች። እነዚህ ብሔሮች በኢህአዴግ ወይም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት የተፈጠሩ አይደሉም። የነበሩና ያሉ በፈጣሪ የተፈጠሩ ናቸው። እናም የኢ.ፌ.ዴ.ሪን መንግሥትና ሕገ መንግሥት እንዲሁም ኢህአዴግን በአገር ከፋፋይነት መክሰስ መሰረተ ቢስ ነው። ኢህአዴግና በኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች የተዘጋጀው ሕገ መንግሥት በተጨባጭ መሬት ላይ ላሉት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እውቅና ነው የሰጡት።
አሁን ያለውን የኢትዮጵያን ቅርፅ የፈጠሩት የቀደሙት የነገሥታት ዘውዳዊ ሥርዓት ኢትዮጵያ የብዝሃ ብሔር አገር ብትሆንም፣ ይህን ብዝሃነት በአንድ የማንነት መለያ በመጨፍለቅ አሐዳዊ አገር የመመስረት ራዕይ ነበራቸው። ዘውዳዊ ሥርዓቱ ይህን ራዕይ ለማሳካት ስትራቴጂ ነድፎ ለመቶ ዓመት ያህል ተግባራዊ አድርጓል። ይሁን እንጂ የዚህ ስትራቴጂ ተግባራዊነት የተለያዩ ብሔራዊ ማንነቶችን አጥፍቶ አንድ ብሔራዊ ማንነት ያላትን ኢትዮጵያ መፍጠር አላስቻለም።
አሃዳዊ ሥርዓት ለመፍጠር በብሔራዊ ማንነቶች ላይ የሚደረገው ጫና እያየለ በሄደበት መጠን የማንነት፣ የእኩልነትና የነፃነት ጥያቄና ትግልም እያየለ ሄዷል። በተለይ ከ1960ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ የተቋቋሙት የተለያዩ ብሔራዊ የነፃነት ንቅናቄዎች የዚህ ማሳያ ናቸው። አሃዳዊ ሥርዓቱን ለመውደቅ ያበቃው ይህ በየአቅጣጫው የተካሄደ የብሔራዊ ማንነት፣ የዕኩልነትና የነፃነት የትጥቅ ትግል ነው።
ከዚህ በኋላ አገሪቱ ሁለት አማራጮች ብቻ ነበሯት። አንደኛው አማራጭ ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነት ዕውቅና ሰጥቶ፣ ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ እርስ በርስ በመከባበር፣ በእኩልነት የሚኖሩባትን የሕዝቦች አንድነት ያላት ኢትዮጵያን መመሰረት ነው። ይህ አሁን በሥራ ላይ ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓት ነው። ሁለተኛው አማራጭ መለያየት ወይም ማንነታችሁ ተጨፍልቆ አንድ መሆን አለባችሁ በሚለው ወገንና በነፃነት ጠያቂ ብሔራዊ ንቅናቄዎች መሃከል ጦርነት ሲያካሂዱ መኖር ነበር።
ከእነዚህ ሁለት አማራጮች የተሻለው ፌዴራላዊ ሥርዓት መስርቶ በአንድነት መኖር ነበር። የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በዕኩልነት የሚኖሩበት ፌዴራላዊ ሥርዓት፣ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያጠናክር እንጂ አገሪቱን የሚከፋፍል ወይም የመገንጠል ጥያቄን የሚቀሰቅስ አይደለም። የፌዴራላዊ ሥርዓት ግብም የኢትዮጵያን አንድነት በማይናወጥ መሰረት ላይ ማቆም ነው።
ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ተግባራዊ በተደረገባቸው ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በአገሪቱ ሰላም ሰፍኗል። የብሔራዊ ነፃነት ግንባሮች የትጥቅ ትግል ከጀመሩባቸው ዓመታት እስከ 1983 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ሰላም አልነበረም። በተለይ ከ1967 እስከ 1983 ዓ.ም የነበሩት አስራ ሰባት ዓመታት አገሪቱ በጦርነት ስትታመስ የነበረችበት ወቅት መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። በእነዚህ አስራ ሰባት ዓመታት መጠናቸው ቢለያይም በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ጦርነት ይካሄድ ነበር። የዚህ ጦርነት መነሻ የነፃነትና የዕኩልነት ጥያቄ ነበር። በእነዚህ አስራ ሰባት ዓመታት ከውጭ ጠላት ጋር ጦርነት የተካሄደው ከየካቲት 1969 እስከ የካቲት 1970 ዓ.ም ለአንድ ዓመት ብቻ ነው፤ ከወራሪው የሶማሊያ መንግሥት ኃይል ጋር።
አገሪቱ በፌዼራላዊ ሥርዓት በተዳደረችባቸው ዓመታት የዕርስ በርስ ግጭቶች ከስመዋል። እርግጥ በፌዴራላዊ ሥርዓቱ በብሔር ላይ ተመስርተው ተደራጅተው ብረት ያነሱ ቡድኖች አሉ። እነዚህ ቡድኖች ክልላዊ መንግሥታት ሥልጣናቸው በቂ አይደለም፤ ከተጽዕኖ አልተላቀቁም በሚል ምክንያት ወደ ትጥቅ ትግል የገቡ ቡድኖች ናቸው። የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦጋዴን ብሔራዊ የነፃነት ግንባር (ኦብነግን) ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ቡድኖች፣ ቆመንላቸዋል የሚሏቸው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች በወከሏቸው የራሱ ልጆች ብቻ የሚተዳደር መሆኑ፣ በፌዴራል መንግሥት ውስጥ በሕዝባቸው ቁጥር ልክ ተወክለው ሥልጣን መጋራታቸው፣ በአስፈፃሚው አካልም ውስጥ የሚሳተፉ መሆኑ፣ ቋንቋቸው የክልላዊ መንግሥታቸው የሥራና የማስተማሪያ ቋንቋ መሆኑ፣ ብሔሮቹ ባህላቸውን እያሳደጉ፣ ታሪካቸውን እየተንከባከቡና ይፋ እያደረጉ ፣ ቋንቋቸውና ባህላዊ እሴቶቻቸው በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ደረጃ የሚጠኑ መሆኑ ወዘተ የያዙትን ዓላማ መሰረተ ቢስ አድርጎባቸዋል። በመሆኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከሙና እየተመናመኑ ሄደው ጥቂት ግለሰቦችን ይዘው በውጭ አገራት ስማቸው ብቻ የሚጠራ ሆነው ቀርተዋል።
በሌላ በኩል ፌዴራላዊ ሥርዓቱ አገሪቱን ለመበታተን አደጋ አጋልጧል በሚል ፌዴራላዊ ሥርዓቱን አፍርሰው አሃዳዊ ሥርዓት ለመመስረት ወደትጥቅ ትግል የገቡ ቡድኖች አሉ። እነዚህም ቢሆኑ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደርና የዕኩልነት መብታቸው በተረጋገጠላቸው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚወከሉ ኢትዮጵያውያንን ድጋፍ ማግኘት ስላልቻሉ በትጥቅ ትግል ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ማድረግ አልቻሉም።
እንግዲህ እነዚህ ከላይ የተገለፁ እውነታዎች ናቸው ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ተኩል በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ያደረጉት። ይህ ሰላም ደግሞ ህዝብና መንግሥት ልማት ላይ የሚያተኩሩበትን ፋታ አስገኝቷል። በተጨባጭ በህዝቡ ኑሮ መሻሻል የተገለፀ ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲሁም ትምህርትና ጤና የመሳሰሉ ማህበራዊ ልማቶችንና መሰረተ ልማት ማስፋፋት ተችሏል። ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በአገሪቱ የተመዘገበው ዕድገት የፌዴራላዊ ሥርዓቱ ውጤት ነው ማለት ይቻላል።
ይሁን እንጂ፣ አልፎ አልፎ ከማንነትና ከወሰን ጋር በተያያዘ ግጭቶች የሚነሱበት ሁኔታ አሁንም ይታያል። በተለይ የአሃዳዊ ሥርዓት ተስፈኞች ይህን ከማንነትና ከወሰን ይገባኛል ጥያቄ ጋር ተያይዞ የሚነሳ አለመግባባትና ግጭት፣ በቀዳሚነት በብሔራዊ ማንነት ላይ የተመሰረተው ፌዴራላዊ ሥርዓት የፈጠረው አድርገው ሲያቀርቡ ይስማማሉ።
በመሰረቱ ሕገ መንግሥታዊው ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ምንም አይነት የማንነትና የወሰን ይገባኛል ጥያቄ የማይነሳበት ያለቀለት ሥርዓት አይደለም። የማንነትና የወሰን ይገባኛል ጥያቄዎች በማንኛውም ጊዜ ሊነሱ እንደሚችሉ ታሳቢ ተደርጓል። እናም ጥያቄዎቹ ሲነሱ ምላሽ የሚያገኙበት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ተቀምጧል። ጥያቄዎቹ ሲነሱ ወደግጭት ከመሸጋገራቸው በፊት በሕገ መንግሥቱ ምላሽ እንዲያገኙ ይደረጋል። ባለፉት ዓመታት ከማንነትና ከወሰን ይገባኛል ጥያቄ ጋር ተያይዞ ግጭቶች ያጋጠሙት፣ ጥያቄዎቹን በወቅቱ ሕገ መንግሥቱ ባስቀመጠው መሰረት ሳይስተናገዱ በመቅረታቸው ነው። እናም ፌዴራላዊ ሥርዓቱ የዕርስ በርስ ግጭት መንስኤ ተደርጎ መወሰድ የለበትም።
እርግጥ በብሔር ላይ የተመሰረተው ፌዴራላዊ ሥርዓቱ በአገሪቱ ለሰፈነው ሰላምና ለተመዘገበው ልማት እንዲሁም ለአገሪቱ አንድነት መሰረት ቢሆንም፣ ከጋራ እሴቶች ይልቅ የተናጥል እሴቶች ላይ ትኩረት የተደረገበት ሁኔታ ታይቷል። ይህ የኢትዮጵያዊነት ስሜት በሚፈለገው ልክ እንዳይጎለብት አድርጓል። በመሆኑም ለልዩነት የተሰጠውን ያህል ትኩረት ለኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴቶችም መስጠት አስፈላጊ ነው።
በአጠቃላይ፣ ኢትዮጵያ በብሔር ላይ የተመሰረተ ፌዴራላዊ ሥርዓት የመሰረተችው ብዝሃ ብሔር ያላት አገር በመሆኗ አንድነቷን ጠብቆ መቆየት የሚያስችል ሌላ አማራጭ ስለሌለ ነው። ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የአገሪቱን አንድነት ለማስጠበቅ በታሪካዊ አስገዳጅ ሁኔታ የመጣ ነው። ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሳትሆን አንድነቷን ጠብቃ መዝለቅ አትችልም። እናም ፌዴራላዊ ሥርዓቱን ማፍረስ ውጤቱ አገሪቱን ማፈረስ ብቻ ነው።

ለሚ ዋቄ

Published in አጀንዳ
Saturday, 12 May 2018 18:07

አተገባበሩ ይፈተሽ!

ኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ሥርዓትን መከተል ከጀመረች 27 ዓመታት ተቆጥሯል። በዚህም ጊዜ ውስጥ አገራችን በርካታ መልካም ነገሮችን ያስተናገደች ሲሆን አልፎ አልፎ ደግሞ ችግሮች መታየታቸው አልቀረም። በተለይም ከወሰን አስተዳደር ጋር ተያይዞ ግጭቶችና መፈናቀሎች ነበሩ። ከማንነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች በተለያዩ ክልሎች ተነስተዋል። እነዚህንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በማንሳትም የፌዴራል ሥርዓቱን የችግር ምንጭ አድርገው የሚቆጥሩ ወገኖች አሉ።
ነገር ግን መታየት ያለበት ችግሩ ያለው ኢትዮጵያ ከተገበረችው የፌዴራል ሥርዓት አደረጃጀት ነው ወይስ ከአተገባበሩ የሚለው ነው። የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም አደረጃጀት እንደሚባለው ሙሉ በሙሉ በቋንቋ ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ በሕገ መንግሥቱ በግልፅ እንደተቀመጠው በአሰፋፈር፣ በቋንቋ፣ በስነ ልቦና እና የህዝበ ውሳኔን ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ነው።
ቋንቋን ብቻ መሰረት ባደረገ መልኩ የተቃኘ ቢሆን ኖሮ ከ76 በላይ ቋንቋ ተናጋሪ ባላት አገር ስንት ክልሎችና የክልል የሥራ ቋንቋ ይኖሩ ነበር ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያህል 56 ብሔር፣ ብሔረሰብ ባለበት ደቡብ ክልል የሥራ ቋንቋቸው አማርኛ ነው፡፡ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከአምስት በላይ ብሔር፣ ብሔረሰቦች አሏቸው፡፡ የእነሱም የሥራ ቋንቋቸው አማርኛ ነው፡፡ በተመሳሳይ የጋምቤላ ክልል የሥራ ቋንቋቸው አማርኛ ነው። የፌዴራሊዝሙ ብቸኛ መሰረት ቋንቋ ብቻ ቢሆን ኖሮ እነዚህ ክልሎች የሥራ ቋንቋቸው አማርኛ አያደርጉም ነበር። በሌላ መልኩ ደግሞ እያንዳንዱ ክልል በራሱ ቋንቋ የመማር፣ የመዳኘት፣ ባህልና ታሪኩን የማሳወቅ መብት አለው። ይሔንና ሌሎች ጉዳዮችን በማየት የፌደራል ሥርዓቱ በቋንቋ ላይ ብቻ የተመሰረተ አይደለም ለማለት ያስደፍራል።
ሌላው ግን በአገሪቱ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ከመተግበሩ ጎን ለጎን ዴሞክራሲ ተያይዞ መጥቷል። ይሄም በአንድ ጊዜ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡ ምክንያቱም የጋራ አመራርና የራስ አስተዳደርን ተግባራዊ ለማድረግ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ያለዴሞክራሲ ሥራ ላይ ሊውል አይችልም፡፡ እነዚህን ለመተግበር ምርጫ ያስፈልጋል፡፡ ሕዝቦች ራሳቸውን የሚመራቸው አካል መምረጥ አለባቸው፡፡ በጋራ አገሪቱን ለመምራትም ወኪላቸውን ያቀርባሉ፡፡ ምርጫ ደግሞ በባህሪያቸው ዴሞክራሲያዊነትን ታሳቢ ያደርጋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ግምት ውስጥ ገብተው ሲታይ የፌዴራል ሥርዓቱ ለኢትዮጵያ አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ነገር ግን አተገባበሩ ላይ አሁንም ችግሮች አሉ፡፡ ዕኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆን ላይ፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የትምህርት ዕድሎችን ባግባቡ ከመጠቀም ከማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች መነሻነት እዚያም ከዚያም ቅሬታዎች ይነሳሉ።
በፌዴራል ሥርዓት በክልል እና በፌዴራል የሥልጣን ክፍፍል አለ። ከዛም አልፎ በአንድ መዋቅር ላይ የሥልጣን ክፍፍል ይኖራል፡፡ የጎንዮሽ፣ የላይና የታች፡፡ ሆኖም ግን በሁሉም ክልሎች የአስተዳደር እርከን የተሟላና ፍትሃዊ የሥልጣን ክፍፍል አይስተዋልም፡፡ ስለዚህ የሥልጣን ክፍፍሉ ሙሉ ለሙሉ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊም እና ሕገ መንግሥታዊም አይደለም ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ግጭት ይቀሰቀሳል። ፌዴራል ሥርዓቱ ግን ይህን መፍታት የሚያስችል ነው፡፡ በአፈፃፀም ረገድ ግን ክፍተት አለ፡፡
ከፌዴራሊዝም ጋር ተያይዞ የሚነሳውና በተግባር ያለው እውነታ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይጣረሳል፡፡ ይህንን በደንብ ማረም ያለበት የፌዴራል መንግሥት ነው፡፡ ምክንያቱም ሕገ መንግሥት የአገሪቱ የበላይ ሕግ ነውና ይህንን የማስከበር ጉዳይ የፌዴራል መንግሥት ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡ በዚህ ረገድ የፌዴራል መንግሥቱ ባለመስራቱ ብዙ ችግሮች ተከስተዋል፡፡ ዜጎች ወደ ፈለጉት አካባቢ ሄደው መስራት፣ ሀብት ማፍራትና መኖር ሥጋት ሆኖባቸዋል። ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስና ሀብት ማፍራት የዜጎች ምርጫ እንጂ የመንግሥት ወይንም የክልሎች ኃላፊነት ወይም ስልጣን ባለመሆኑ፤ በዚህ ረገድ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች መሰረታቸው ሕገ መንግሥታዊም ህጋዊም ባለመሆኑ መታረም አለበት።
በአጠቃላይ ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ የታዩ ችግሮች አንድ ሁለት ተብለው ሲቆጠሩና ሲመዘኑ መነሻቸው ኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት በመተግበር የተፈጠሩ ሳይሆን አተገባበሩ ላይ የነበረ ችግር መሆኑ ቁልጭ ብሎ ይታያል። ስለዚህ ሁሉም ወገን ሊረዳና ሊወስድ የሚገባውም እውነታ ይሄው ነው። አሁንም ችግሩ ያለው በሥርዓቱ ላይ ሳይሆን በአተገባበሩ ላይ በመሆኑ ይሄ በደንብ ሊፈተሽ ይገባል።

Published in ርዕሰ አንቀፅ

ሰፊው ግቢ የረጅም ዕድሜ አሻራ የሚታይባቸውን በርከት ያሉ ቤቶችን ይዟል። በውስጡ የሚንቀሳቀሱ ጥቂት ሰዎች ይታያሉ፡፡ የግቢው ንጣፍ ድንጋይ ሳር በቅሎበታል።ይሄ በመሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡ ቤቱ በ1940ዎቹ መጀመሪያ በልእልት ተናኜወርቅ ሴቶችን በዕደ ጥበብ ለማሰልጠን ታስቦ የተቋቋመ ነበር። ይህ ዕድሜ ጠገብና ታሪካዊ ተቋም ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲሰራ የኖረውንና የተቋቋመበትን አላማ አቁሟል። የተወሰኑ ቤቶች ከነቁሳቸው በቁልፍ ተከርችመዋል።ቀሪዎቹ ተከራይተዋል፡፡ 

ላለፉት ሁለት ዓመታት ታሽገው ከተቀመጡት መካከል የልብስ ስፌት ማሽኖች ፣የተዘጋጁ ልብሶችና ሌሎች ቁሶች ይገኛሉ። ማሽኖቹ ምንም ችግር የሌለባቸው በመሆናቸው አገልግሎት ላይ ሊውሉ የሚችሉ መሆናቸውን ሰምተናል።
በተቋሙ ከ30 ዓመት በላይ ያገለገሉትንና በአሁኑ ወቅት በግቢው ውስጥ በኪራይ ምግብ ቤት ከፍተው እየሰሩ ያገኘናቸው ወይዘሮ አብነት ፋንታሁንና ወይዘሮ ሙሉወርቅ ካሳ እንዲህ ይናገራሉ፡፡ በ2008 መጨረሻ አካባቢ ተቋሙ ሥራውን ያቆመው ስለከሰረና ራሱን ማስተዳደር ስለማይችል በሚል ምክንያት ነበር። ጡረታቸው የደረሰ በጡረታ፤ ለሌሎቻችን ደግሞ እንደየደረጃችን የአገልግሎት ተሰጥቶን ተሰናብተናል ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ወርቅነሽ ወልደየሱስ በበኩላቸው እንዳሉት « ሠራተኞቹ አቅማቸው አነስተኛ በመሆኑና ከጊዜው ጋር ተወዳዳሪ ሆነው መቀጠል አልቻሉም። በ2004 ፌዴሬሽኑ ተቋሙን ሲረከበውም ኪሳራ ውስጥ ነበር » ብለዋል።
እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ ፌዴሬሽኑ ከተረከበው ጀምሮ ሴቶቹን ውጤታማ ለማድረግ በርካታ ሙከራዎች ቢደረጉም አልተሳካም። በፊትም ቢሆን አትርፈው ሳይሆን ደመወዛቸውን ጨምሮ ሌሎች ወጪዎች የሚሸፍኑት ከቤት ኪራይ ነበር ።በዚህም መንገድ ሊሳካላቸው ስላልቻለ ከድሮ ጀምሮ የነበረውን ተቀማጭ እስከመጠቀም ደርሰዋል።
ፌዴሬሽኑ ተቋሙን የተረከበው አትርፎ እንደ አንድ የገቢ ምንጭ ለማድረግ ነው። ንብረትነቱም የ8 ነጥብ 5 ሚሊዮን የማህበሩ አባላት በመሆኑ እየከሰረ ይቀጥል ማለት አይቻልም። በመሆኑም እንዲዘጋና ሠራተኞቹ አስፈላጊው ክፍያ ተከፍሏቸው እንዲሰናበቱ፤ መቀጠል የሚፈልጉ ካሉ ተደራጅተው ከተቻለ በግቢው ውስጥ በነጻ ካልሆነም በመጠነኛ ኪራይ ባሉት የስፌትና የሽመና እቃዎች እንዲሰሩ ዕድል ተሰጥቷል።ሆኖም ግን አብዛኛዎቹ የጡረታ ጊዜያቸው ስለደረሰ ጡረታቸው ተከብሮ ተሰናብተዋል።የተወሰኑት በግቢው ውስጥ እየሰሩ ይገኛሉ። በወቅቱ በልብስ ስፌት ሥራ እንቀጥላለን ብለው ለተደራጁት ማሽኖቹን ለመስጠት ስንነሳ ግን የበጎ አድራጎት ድርጅት «እናንተ የተቋቋማችሁት በፌዴራል ደረጃ ስለሆነ መስራት ያለባችሁ የማስተባበር ሥራ ነው። ይሄን መስራት ያለበት በከተማ አስተዳደሩ ያለው ፌዴሬሽን ነው» የሚል ምላሽ ተሰጠ።የተበተኑትም ሴቶች በአዲስ አበባ ሴቶች ፌዴሬሽን በኩል ተደራጅተው እንዲደገፉ ስምምነት ላይ ተደረሰ።በቀጣይ ግን ለአዲስ አበባ ሴቶች ፌዴሬሽንና በሥራችን ላሉት ማህበራትም ማስተላለፍ አትችሉም አቁሙ ተባልን። ከዚህ በኋላ በርካታ ምልልሶችን ብናካሂድም ቁርጥ ያለ ምላሽ ማግኘት አልተቻለም ይላሉ።
ውዝግቡ እንዳለ ሆኖም ፌዴሬሽኑ ማዕከሉ ሲቋቋም ጀምሮ የነበሩ የተለያዩ የሙዚቃ መሳሪያዎች፣ የመመገቢያ እቃዎችን ጨምሮ በዕደ ጥበብ ዘርፍ በታሪካዊ ቅርስነት ሊጠበቁ የሚገባቸው ንብረቶች በሙሉ መዝግቦና ለብልሽት እንዳይዳረጉ በጥንቃቄ ማስቀመጡን ይናገራሉ። በቀጣይም ቦታው ላይ በሚገነባው ህንፃ ውስጥ ሙዚየም በማዘጋጀት ለቅርስነት ለመጠቀም ታስቧል። ነገር ግን እስከዚያም ቢሆን ፌዴሬሽኑ ገቢ ማግኘት ስላለበት የተወሰኑ ቤቶች ተከራይተዋል።
በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ የንብረት ማጣራት ማስተላለፍና ማስወገድ ዳይሬክተር አቶ ዳኜ ሽብሩ በበኩላቸው ዕቃው ታሽጎ መቀመጥ የለበትም። እነሱንም ከመጠቀም የሚያግዳቸው ነገር የለም ይላሉ፡፡ በ2008 ጥያቄ ሲያቀርቡ በአካልም መጥተው የተነጋገርነውና የተግባባነው ቅርንጫፍ ካላቸውና እነሱ የሚከታተሉት ከሆነ መስጠት እንደሚችሉ ነው።
በተጨማሪም ተደራሽ ያልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን አሰልጥነንና አብቅተን እናወጣለን፤ ሴቶችን ራሳቸውን እናስችላለን፤ የሚል ፕሮጀክት ካላቸው ማስተላለፍ መብታቸው ነው። ለራሳቸው ለፌዴሬሽን ቅጥር ሰራተኛ ማስተላለፍ ግን አይችሉም። በዚህ በኩል አሁንም ቢመጡ የሚስተናገዱ ይሆናል። የህዝብን ሀብት አላግባብ እንዲቀመጥ ማድረግ ግን ራሱ የሚያስጠይቅ ነው ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

ዜና ሐተታ
ራስወርቅ ሙሉጌታ

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።