Items filtered by date: Sunday, 13 May 2018

ይህ ሰው በኢትዮጵያ አግር ኳስ አፍቃሪ ልብ ውስጥ በብዙ የሚታወስ ነው። እግር ኳስን ከልጅነት እስከ እውቀቱ ተጫውቷል። አሁንም ቢሆን ከክቧ ኳስ አልራቀም። የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ የቡድን መሪ ነው። ባዩ ሙሉ። የመጀመሪያውን የምሥራቅ አፍሪካ የታዳጊዎች ቻምፒዮና ለኢትዮጵያ ዋንጫ ይዘው ከመጡ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሲሆን በጊዜው የእርሱ ድርሻ ጉልህ ነበር።
ከዚህም ሌላ ኬንያ ባዘጋጀችው «የሴካፋ ቻምፒዮና» ላይ ኮከብ ተጨዋች ሆኖ ለመመረጥም በቅቷል። የምሥራቅ አፍሪካ ውድድር ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአገር ውጪ በሩዋንዳ ዋንጫ ስታነሳ በፍፃሜው ጨዋታ ላይ የማሸነፊያዎቹን ሁለት ግቦች አስቆጥሯል። ባዩ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለት ዓመት በዋናው ክለብ ተሰልፎ ተጫውቷል። በፕሮፌሽናል ተጫዋችነትም ቢሆን በር ከፋች ነው። በቤልጂየም አገር ለረጅም ጊዜ ለተለያዩ ክለቦች ተጫውቷል። አንጋፋዋ የቀበና ቤሌር ሜዳ ካበቀለቻቸው የአገር ባለውለታዎች ተርታም የሚመደብ ነው። እኛም ለዛሬ የዚህን ተጫዋች ህይወት በእሁድ እንግዳችን ላይ በስፋት ለመዳሰስ ወደድን።
የልጅነት ትውስታ
የቤሌር ሜዳ በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ ተወላጆች ዘንድ ትልቅ ቦታ አለው። ቀበና መድኃኒ ዓለም ቤተክርስቲያን አካባቢ የሚገኘው ይህ ስፍራ በርካታ አንጋፋ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን አፍርቷል። የያኔው ታዳጊ ባዩ ደግሞ ከዚህ ሜዳ ጀርባ በሚገኙ መንደሮች ውስጥ በአንዱ ነበር ተወልዶ ያደገ ሲሆን ጊዜውም 1971 ዓ.ም ነው።
ለቤሌር እግር ኳስ ሜዳ ቅርብ መንደር ውስጥ የተወለደው ባዩ «ቤታችን እና የቤሌር ሜዳ በጣም ተቀራራቢ ነው። መሀል የእግር ኳስ ሜዳው መኖሪያችን እንደሆነ ይሰማኝ ነበር» በማለት የልጅነት ጊዜውን እግር ኳስ እየተጫወተ እንዲያድግ ትልቅ ምክንያት እንደሆነው ይገልፃል። ቤሌር በርካታ አንጋፋ ተጫዋቾች የወጡበት ነው። ሜዳው እግር ኳስን ከንጋት ጀምሮ ሰማዩ ለአይን እስኪይዝ ድረስ የአካባቢው ተወላጆች እና ከሌላ ሰፈር የሚመጡ ታዳጊዎች የሚጫወቱበት ነበር።
«ንጉሴ ገብሬ፣ ሰለሞን ሀይለ ማሪያም፣ሲሳይ ሽፈራው የመሳሰሉ አንጋፋ ተጫዋቾችን ተመልክቼ ኳስ እያቀበልኩ ነው ያደኩት» የሚለው ባዩ እግር ኳስ በልጅነት ልቦናው ውስጥ ትልቅ ስፍራ እንዲኖረው አንጋፋ ተጫዋቾች ድርሻ እንደነበራቸው ይናገራል። በወቅቱ ለቤሌር ታዳጊዎች እግር ኳስ ከምንም ነገር በላይ ነው። እንደ መዝናኛ፣ ጊዜ ማሳለፊያ እና ተስፋ ያለው ጎበዝ እግር ኳስ ተጫዋች የመሆን ህልምን እንደማሳኪያ ያገለግል ነበር። በዚህ እድል ውስጥ ያለፈው ባዩ በፍቅር ከሚያንከባልላት ኳስ ጋር የእድሜ ዘመን ወዳጅነትን መስርቷል።
«ከትምህርት ቤት መልስ ሁሌም እንዲሁም በእረፍት ቀን በሰፈራችን ቤሌር ሜዳ ላይ ከእድሜ እኩዮቻችን ጋር እንጫወታለን። ውድድሮችን ከሌሎች የአካባቢ ልጆች ጋር እናደርጋለን» በማለት የእነ ንጉሴ ገብሬን ፈለግ በመከተል ከአቻዎቹ ጋር የቤሌርን ሜዳ በእግር ኳስ ጨዋታ ያደምቋት እንደነበር ከትውስታው ማህደር እየገለጠ ይናገራል። የአካባቢው ሰዎች እና እግር ጥሏቸው በስፍራው የሚያልፉ ሰዎች የነባዩን ፍልሚያ ልክ እንደ ስታዲየም በመክበብ ይመለከቱ ነበር። ይህ ደግሞ ለታዳጊው ትልቅ ተጫዋች ለመሆን ህልም ለነበረው ባዩ ትልቅ የሞራል ስንቅ ነበር።
አካባቢው በውድድር ይደምቃል። እናቶች ልጆቻቸውን ለማበረታታት የማጀት ስራቸውን ጥለው ቤሌር ሜዳን ይከቧታል። በስፍራው ለመገኘት ከቤት ሁለት እርምጃ እግርን ማንሳት ብቻ በቂ ነበር። በዚህ ስፍራ እግር ኳስን ተጫውቶ እንዲያሸንፍ ከመፈለግ ውጪ ቤተሰብ ልጁን ወደ ሜዳ እንዳይሄድ አይከለክልም። ይልቁንም ውድድር እና ልምምድ ሲኖር ድጋፍ ያደርጋሉ። እግር ኳስ ለዚህ መንደር አንዱ ማህበራዊ ህይወት የሚጠናከርበት፤ ከእቁብ እና እድር ተለይቶ የማይታይበት ጭምር ነው። ታዲያ እነ ባዩም ወላጆቻቸውን አያሳፍሩም፤ ለውድድር የመጡ የሌላ ሰፈር ልጆችን ድል ማድረግ እና የመንደር ዋንጫዎችን መሰብሰብ ልማዳቸው ነበር። ምክንያቱም በቤሌር ማሸነፍ ከልማድም በላይ ነው።
«ሰፈሬ ላይ እግር ኳስን ተጫውቼ ማደጌ ለስኬቴ ትልቅ በር ከፍቶልኛል። በጊዜው በሄድንበት ሰፈር ሁሉ እንታወቅ ነበር» በማለት ባዩ የልጅነት ትዝታው ለዛሬው ስኬታማ የእግር ኳስ ህይወቱ ዋናውን በር እንደከፈተለት ይናገራል። በሰፈር ውስጥ የላስቲክ እና ጨርቅ ኳስ በማንከባለል የተጀመረው የእግር ኳስ ህይወት ተስፋ ሰጪ እና አዲስ መስመር ከፍቷል። ሜዳው በቀላሉ የሚለቅ አይደለም። «ያደቆነ ሴይጣን ሳያቀስስ አይለቅም» እንደሚባለው ብሂል ባዩ ሙሉ ህይወቱ በእግር ኳስ እንዲያሳልፍ እድል የሚከፍቱ ምልክቶች መታየት ጀመሩ። ክህሎቱ እየጨመረ ሄደ፤ ኳስ ከቀልጣፋ እግሮቹ ጋር ፍቅር እየያዛት፤ እሱም በርሷ እየተሳበ ሂደቱ እየከረረ መጣ።
አዲስ መንገድ
ባዩ የ7ተኛ ክፍል ተማሪ ሆኗል። 12ተኛ ዓመቱንም ይዟል። በሰፈሩ እግር ኳስ ውድድሮችን ቀበሌ ያዘጋጅ ነበር። በየእድሜ ደረጃው ቡድኖች ተዋቅረዋል። እሱ እድሜው ገና ቢሆንም የእግር ኳስ ችሎታው ጥሩ ስለነበር በ«ቢ» ቡድኑ ውስጥ ሊመረጥ ቻለ። የእድሜ ልዩነቱ እጅግ ሰፊ ቢሆንም አብሯቸው ልምምድ ያደርግ ነበር። ለአንድ ዓመት ያክል በዚህ ስብስብ ውስጥ ውድድሮችን እና ልምምድ ሲሰራ ቆየ። ሆኖም ግን ቡድኑ በተለያዩ ምክንያቶች ፈረሰ። እነ ባዩም የመበተን አደጋ ገጠማቸው። ነገር ግን የሰፈር ልጆች ተሰባስበው

 

 ዳግም ከበደ

 

 

 

Published in ስፖርት
Sunday, 13 May 2018 17:44

ጀግና የሆንኩበት ቀን

ጀግና የሆንኩበት ቀን

ለካ ጀግንነት እንዲህ ያደርጋል እንዴ ጎበዝ? ለአንድ ቀን ጀግና ሆኜ እኮ ነው እንዲህ የምለው፤ ሁሌም ጀግና ሆኜ ቢሆን ኖሮማ ጉራዬ አያስቀምጥም ነበር፡፡ ለነገሩ ጀግና እኮ ግን ጉረኛ አይደለም፤ እኔ ግን ጉረኛ ሆንኩ፡፡ በቃ እንዲያውም ጀግና አልነበርኩም፡፡ ግን ለሰዓታት ያህል ትንሽ እንደ ወኔ ነገር ተሰምቶኝ ነበር፡፡ ታዲያ በዚያች ቅጽበት ውስጥ ‹‹ለካ ጀግንነት እንዲህ ነው›› ብዬ ነበር፡፡ አይ ጀግንነቴማ በዚያች ቅጽበት ተወስኖ አይቀርም!

ወደ ቁም ነገሩ ስንገባ ባሳለፍነው ሳምንት ሚያዚያ 27 የአርበኞች ቀን ሲከበር በጠዋት ነበር አራት ኪሎ አደባባይ የተገኘሁት(ጀግና መሆኔ እኮ ነው) እናላችሁ በዕለቱ በጣም ብዙ ነገር ነው ያስተዋልኩት፡፡ አንዱ የታዘብኩት ነገር ‹‹ወጣቱ ታሪኩን ረስቷል!›› የሚባል ወቀሳ ውሸት መሆኑን ነው፡፡ ኧረ ጎበዝ መወቃቀስ ብቻ ሳይሆን እየተደናነቅንም ይሁን! ይህን ጊዜ እኮ ይሄ ወጣቱን የሚወቅስ ሁሉ እሱ ያላደረገውን ነገር ይሆናል፡፡

አሁን እኔም ወቀሳዬን ልተውና ወደ ጉዳዬ! እና እንዳልኳችሁ በጠዋት ነበር የተገኘሁት፡፡ ብዙም ሳይቆይ አባት አርበኞች በሰልፍ በሰልፍ እየሆኑ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡ መጡ፡፡ አባት አርበኞችን ሳይ ልክ አብሬ የዘመትኩ ነበር የመሰለኝ፡፡ አባት አርበኞችንና እንግዶችን ለማድመቅ ደግሞ የፖሊስ ማርሽ ባንድ ቡድን ጥዑመ ዜማ እያሰማ ነበር፡፡ አቤት እኔ ደግሞ የማርሽ ባንድ ሰልፍ ደስ ሲለኝ፡፡ የአገራዊ ዘፈኖችን ዜማ እያሰሙ አደባባዩን ሲያደምቁት ቆዩ፡፡

አሁን ነው እንግዲህ ዋናው ወኔዬ የተቀሰቀሰላችሁ፡፡ ዋናው ፕሮግራም ሲጀመር የአባት አርበኞች ፉከራ ተጀመረ። እነርሱን ለማጀብ ደግሞ ወኔ ቀስቃሽ ሙዚቃ ሲለቀቅ ምን እንደሚፈጠር አስቡት፡፡ ‹‹አሁን ይሄ ደግሞ ምን አደረኩ ብሎ ነው?›› ይሉኛል ብዬ ነው እንጂ መሃል ገብቼ ‹‹አካኪ ዘራፍ» ማለት አምሮኝ ነበር፡፡ ቆይ ግን ጦር ሜዳ የተሰለፈ ብቻ ነው እንዴ መፎከር ያለበት? የአባቶች ጀግንነት ብቻ እኮ እኔን ቢያስፎክረኝ በቂ ነው፡፡ በተለይማ የአባት አርበኞችን ፉከራ ሌሎች ሰዎች ሲያጅቡት ሳይ ‹‹በቃ አሁን ነው መፎከር ያለብኝ›› ብዬ ነበር፡፡ ልቤ በጀግንነት ሙልት አለ፡፡ እንዲያውም የዚያን ጊዜ ግራዚያኒ አጠገቤ ቢኖር ከአብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የተረፈውን እጁን ጠምዤ ነበር የምጠለው(አቤት ጉራ!)

እንዴት አያችሁት ግን የኔ ጀግንነት? የስካር ጀግንነት ይመስላል አይደል? ደግሞ ሰክሬ አላውቅም በሉ፡፡ ቢያንስ ቢያንስ አንድ ቀን(በልጅነቱም ቢሆን) የሰከረ ይኖራል፡፡ እሺ ግድየለም ጭራሽ ሰክሮ የማያውቅ ሰው ካለም የሰከረ ሰው አይቶ ያውቃል፡፡ ከዚህ ሁሉ ያለፈ ካለ እንግዲህ እኔ ሰክሬ ስላማውቅ እነግረዋለሁ፡፡ የስካር ጀግንነት ማለት ስካሩ እስከሚያልፍ ብቻ ያለ ማለት ነው፤ ስካሩ ሲለቅ አብሮ ይለቃል፡፡ ራሱ በስካሩ ወቅት ያለው ጀግንነትስ ልክ የሆነ ጀግንነት ቢሆን ደግ አልነበር? ሳይደርሱበት ይደርሳል፤ ሲደርሱበት ደግሞ በስካር ስለተጎዳ ተልፈስፍሶ ይወድቃል፡፡

ታዲያ የኔ ጀግንነት ከስካር ጀግንነት ጋር ምን አገናኘው? የሚያገናኘው ነገርማ ከዚያ ስወጣ ይደገማል ወይ? የሚለው ነው፡፡ ‹‹እንግዲህ እሱን አንተ ታውቃለህ›› ካልችሁኝ እመኑኝ እደግመዋለሁ (ይህኔ እኮ በጦርነት የሚመስለው የዋህ ይኖራል)፡፡ ምስጋና ለጀግኖች አያት ቅድመ አያቶቼ እንጂ ማንም የማይደፍራት፤ በጀግንነት ስሟ እንደተጠራ የምትኖርና ሰላምን እንጂ ጦርነት የሌለባት አገር እኮ ነው ያስረከቡኝ፡፡ ታዲያ የኔ ጀግንነት ምን ይሁን?

እንግዲህ የኔ ጀግንነት የሚሆነው አባቶች ያስረከቡኝን አገር መረከብ ነዋ! መረከብ ማለት ዝም ብሎ መቀበል ብቻ አይደለም፤ ልክ እንደ እነርሱ ነጻ የሆነች አገር ለልጅ ልጆቼ ማስተላለፍ ነው፡፡ ወይኔ! የልጅ ነገር ቢነሳ ሚስት ትዝ አለኝ፡፡ ታዲያ ምን ይሻላል? አይ እንግዲህ አሁን የአገር ጉዳይ እያወሩ ሌላ ሀሳብ መደንቀር ምን ይሉታል? በቃ ስለሚስትና ልጅ ሌላ ጊዜ እናወራለን፤ አሁን ወደጀመርነው ጉዳይ!

የእኛ የወጣቶች ጀግንነት መሆን ያለበት ነጻ የሆነች አገር ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ነው፡፡ ነጻ የሆነች አገር ማለት ግን ምን ማለት ነው? መቼም የግድ የጦርነት ወራሪ ብቻ መሆን የለበትም አይደል? እንዲያውም ከባለሥልጣኖች ደጋግመን እንደምንሰማው ድህነት ወራሪ ሃይል ሆኗል አሉ፡፡ ስለዚህ ለቀጣዩ ትውልድ ከድህነት ነጻ የሆነች አገር ማስረከብ፡፡ ከድህነት ብቻ ሳይሆን ከመሃይምነት ነጻ የሆነች አገር መስጠት ነው።  ‹‹የድህነትን ተራራ የሚንደው ጥይት ትምህርት ነው›› ብለው ነበር አቶ መለስ ዜናዊ። ትምህርት እኮ ለመሃይምነት የምር ጥይት ነው(ኧረ እንዲያውም ድማሚት ነው)፡፡

ቆይ ግን ድህነትን እንዴት ነው ማሸነፍ የሚቻለው? ጠንክሮ በመስራት፡፡ ‹‹ታዲያ ይሄን ማን ያስተዋል?›› የሚል እኮ ይኖራል፡፡ እውነት አሁን እኛ አገር ጠንክሮ የመስራት ባህል አለን? እስኪ እንተዛዘብ ጎበዝ! ካላንደር የሚዘጋበት ቀን ቅዳሜ ወይም እሁድ ቀን ሲውል የምንናደድ የለንም? ይሄ እኮ ላለመስራት ነው፡፡ በሥራ ቀን እንዲሆንና ቤት ለመዋል እኮ ነው፡፡ ትምህርት ቤት እያለን እንኳን ‹‹ነገ ትምህርት የለም›› ሲባል እንዴት ነበር የምንፈድቀው? ጠንካራ የትምህርት ፍላጎት ያለው ተማሪ እኮ ‹‹ትምህርት የለም›› ሲባል ነው የሚናደደው፡፡

ኧረ ቆይ ራሱ ሥራ ቦታ ያለውንም መዝረክረክ እናውራው! በሞቴ እንዲያው አለቃችን ካላየን በሻይ ሰበብ ከቢሮ የምንወጣበት ምክንያት አይበዛም? እሺ እሱም ይሁን አለቃችን ዝም ቢለንና በቢሮ ውስጥ የስም መቆጣጠሪያ ባይኖር ሥራ ቀረ ብለን እንቆጫለን? ለሥራው ፍቅር ቢኖረን ኖሮ ግን የስም መቆጣጠሪያ የሚባል ነገር አያስፈልግም ነበር፡፡

አሁን ወደ መጀመሪያው ጀግንነቴ ልመልሳችሁ፡፡ ሚያዚያ 27 ቀን በአራት ኪሎ አደባባይ ብቻ አልነበረም ጀግና የሆንኩ፡፡ ወደሥራ ቦታዬ ስሄድ ራሱ መንገዶች ሁሉ የባህል ልብስና የጀግኖች ምስል ያለበት ቲሸርት በለበሱ ወጣቶች አገራዊ ወኔን የሚቀሰቅስ ነበር፡፡ ይሄም ብቻ አልነበረም፤ ማታ ወደቤቴ ገብቼ ራሱ የመገናኛ ብዙኃን ጣቢያዎች በሙሉ ስለዕለቱ ሲያወሩ ነበር፡፡ እዚህ ላይም የታዘብኩት ነገር የመገናኛ ብዙኃን ለታሪክ የሚሰጡት ሽፋን ደካማ ነው የሚለው ወቀሳ እየከሸፈ መሆኑን ነው፡፡ በነገራችን ላይ ወቀሳ አንድ ጊዜ ከተጀመረ እኮ ዝም ብሎ ይሄዳል፡፡

አንድ ሰው ‹‹የአገራችን መገናኛ ብዙኃን ለታሪክ ሽፋን አይሰጡም!›› ሲባል ከሰማ ሁሌም እውነት ይመስለዋል፡፡ አንድ እንኳን መገናኛ ብዙኃን ሳይከታተል በዘፈቀደ ‹‹አይሸፍኑም›› ብሎ ይናገራል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ አንዱን ብቻ ይሰማና አስተያየቱ ለሁሉም መገናኛ ብዙኃን ይሆናል፡፡ ሁሉም እኮ አንድ አይነት አይሆኑም፤ የየራሳቸው አሰራር ያላቸው ናቸው፡፡ አሁን ዋናው ጥያቄ የዚያን ዕለት የነበረኝን ጀግንነት እንዴት ላስቀጥለው ነው?

እንዴት አሰብኩ መሰላችሁ? የአገሬን ታሪክ ለማወቅ ማንበብ፤ ማስነበብ፡፡ ቀጥሎም ጎበዝ ሠራተኛ መሆን፡፡ እንዲያውም እኮ ጎበዝ ሠራተኛ ብሆን ተሸላሚ ልሆን እችላለሁ፡፡ ተሸላሚ ደግሞ እንደምታውቁት ጀግና ነው፡፡ ምን አለ በሉኝ ከዛሬ ጀምሬ ጎበዝ ሠራተኛ ባልሆን! በቃ የወረረኝ ጀግንነት ሳይለቀኝ ነው የወሩን ሥራ አጥረግርጌ በአንድ ቀን የምሰራው፡፡ ‹‹ያዝልቅልህ›› አትሉኝም?

ዋለልኝ አየለ

ሱሪው

አዛውንቱ እጃቸው ላይ ብር አጥሯቸዋል። በመሆኑም ሳምንቱን ሙሉ የት እንደሚያመሹ ግራ ተጋብተዋል። እናም ካላቸው ሁለት ሱሪዎች መካከል የጓደኛቸው ልጅ ከውጭ አገር ያመጣላቸውን ሱሪ አስቀርተው ሌላኛውን ሱሪ በሰፈራቸው ለሚገኝ ልብስ ቤት በ70 ብር ይሸጣሉ። በአስር ብሩም  የደንቡን ሶስት ብርሌ ጠጅ በላይ በላዩ ገልብጠው እያጋሱ ወደቤታቸው ይመለሳሉ። በእለተ ቅዳሜ 10 ሰዓት ገደማ የወጡት አቶ አበበ በጊዜ ወደ ቤታቸው አልተመለሱም። ምክንያቱም ድንገት በመንገድ ላይ እያሉ እጃቸውን ወደ ኪሳቸው ቢሰዱ 60 ባውንዳቸው የውሃ ሽታ ሆኖባቸዋል።

 ከጠጅ ቤቱ ወደቤታቸው እስኪጓዙ ድረስ ግማሽ መንገዳቸውን ቢያገባድዱም የረገጧትን መንገድ እየተመላለሱባት አቀርቅረው ብራቸውን ሲፈልጉ አንድ ሰዓት ያህል ይፈጅባቸዋል። ጨለማው በመበርታቱም ብራቸውን እንደተበሉ አሰበው እየተበሳጩ እና እየተቆናጠሩ በእግራቸው ወደቤታቸው መኳተኑን ተያይዘውታል።

የሰፈራቸውን አስፓልት መንገድ ላይ ሲደርሱ ግራ ቀኝ አማትረው መሻገሩን እረስተው አውራ ጎዳናው ላይ ዘው ቢሉ ሁለት በተቃራኒ አቅጣጫ ይጓዙ የነበሩ ታክሲዎች በአንድነት የተጠንቀቁ ጥሩንባ ድምጻቸውን አምባረቁባቸው። አቶ አበበ ይህን ጊዜ ደንገጥ ብለው መኪናዎቹን ካሳለፉ በኋላ የሰፈራቸውን የኮብልስቶን መንገድ ተያያዙት። በፍጥነት ቤታቸው እንደደረሱ በየስርቻው ብራቸውን መፈላለጉን ቀጠሉ። ባለቤታቸው ወይዘሮ አሰገደች ግን ምን እንደሚፈለጉ በውል ባለማወቃቸው «አቶ አበበ ምነው ዛሬ ቆዩ፤ አሁን ምን እየፈለጉ ነው» የሚል ቀጭን ድምፃቸውን አሰሙ።

 በዚህ ወቅት አቶ አበበ ንዴታቸውን ባለቤታቸው ላይ ለመወጣት «እስቲ ዝም በይ፤ ገንዘብ ጠፍቶብኝ ነው፤ ከቤት ስወጣ ኪሴ ውስጥ ነበር ስመለስ ግን የለም» አሉ። «ታዲያ ሲሄዱ ከነበረ እኪስዎ ውስጥ እንጂ አሁን እቤት ውስጥ መፈለጉ ምን ያደርጋል መንገድ ላይ ጥለውት ነው የሚሆነው። ለመሆኑ ምን ያህል ብር ነው?» አሉ ወይዘሮ አሰገደች።

አቶ አበበ ግን ትናንትና ማታ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው የቡና መግዣ ሲጠይቋቸው ኪሴ ውስጥ ያለው 20 ብር ብቻ ነው ማለታቸው ትዝ ስላላቸው ስንት ብር እንደጠፋቸው ለመናገር አልቻሉም። የጠፋብኝ ብር 60 ነው ቢሉ እሰይ ማታ ስጠኝ ስልህ ታዲያ ምነው ተስቆነቆንክ እንደሚባሉ ያውቁታልና ዝም ማለትን ነበር የመረጡት። «ብዙ ብር ነው እንዴ አሉ» ወይዘሮ አሰገደች ደግመው እንዲያናግሯቸው በመፈለግ። አባወራው የማታውን ቅጥፈታቸውን የሚሸፍን ምክንያት ያገኙ ይመስል «አዎ ማታ ሰው ሰጥቶኝ ነበር የሰው ብር ጠፋብኝ 60 ብር ነው። አንድ አብሮኝ የሚሰራ ጓደኛዬ ከማጠፋው አንተ ጋር ይቀመጥልኝ ብሎ ቢሰጠኝ እኔው አጠፋሁት፤ እስቲ አሁን አትጨቅጭቂኝ ብሩን ብቻ ፈልጊ» ብለው ሶፋውን ያገለባብጡ ጀመር።

የቤቱ እመቤት ግን «አይ እዚህ እንኳን የለም እኔ ቤቱን ጠርጌ ወልውዬዋለሁ የቤቱን መረገጫ ላስቲክ ውጪ ወይ ሌባ መንትፎት ይሆናል» ብለው ወደጓዳቸው ገቡ። ነገሩ በዚሁ ታለፈና በሶስተኛው ቀን አቶ አበበ በቤታቸው ያለውን እንደእንቁ የሚያዩትን አንድ ሱሪያቸውን አውልቀው በቁምጣ ሆነው እንዲታጠብላቸው ለቤቱ ሰራተኛ ይሰጧታል። ታዲያ ይህች ሰራተኛ ልብሱን ከማጠቧ በፊት ኪሱን መፈታተሽ ነው የመጀመሪያ ስራዋ። ሁሉምን ኪሱን ፈትሻ ስትጨርስ ምንም ነገር የለም ሱሪውንም አረፋ ወደደፈቀው የሳፋ ውሃ ውስጥ ጨምራ አንዴ አሸት እንዳደረገች ግን ከወደእግሩ አካባቢ ይቆረቁራታል።

ሱሪውን አውጥታ በውስጥ በኩል ብታየው ገበሩ ነጭ ነበርና ብሩን ቁልጭ አድርጎ ያሳያታል። የሱሪው ኪስ በመቀደዱ ምክንያት እግሩ ጋር የደረሰው ብር ለማውጣት እጇን የሚያሳልፍ አልሆን ቢላት የሱሪውን ስፌት በሙሉ ተርትራ 60 ብሩን አወጣችው። ጀብዱ እንደሰራ ሰው «ጋሽዬ ጋሽዬ እያለች ሮጣ ሱሪዎ ውስጥ ብር ተገኝቷል» ብላ የረጠበውን ብር ሰጠቻቸው።

አቶ አበበ ወዲያው የጠፋባቸው ብር እንደሆነ ገብቷቸው ደስታውን አልቻሉትም ነበር። ወይዘሮ አሰገደች ግን ሰራተኛቸው ብሩን ስታገኝ ቅድሚያ ለእርሳቸው መስጠት እንደነበረባት እያሰቡ ውስጣቸው ቂም መቋጠር ጀምሯል። ቀስ ብለው ልጅቷ የምታጥብበት በረንዳ ላይ ሄደው «ብሩን እንዳገኘሽ መጀመሪያ ለእኔ ለምን አልሰጠሽኝም ስንት የሚገዛዛ ነገር እያለ አንቺ ደነዝ» ብለው ወረዱባት። ልጅት የጥፋተኝነት ስሜት እየተሰማት ይቅርታ ጠይቃ አጎንብሳ ማጠቧን ቀጠለች።

አቶ አበበ እና  ባለቤታቸው ከብሩ መገኘት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት ተገናኝተው አይነ ለአይን እየተያዩ ነው። «እሰይ እሰይ ብሩ ተገኘ በሉ ለእኔም ሃምሳዋን ብር ይስጡኝና የሚገዛዛውን ለቤቱ ልግዛ» አሉ ወይዘሮዋ።

አቶ አበበ «የሰው ብር ሲገኝ ይመለስ ይባላል እንጂ እናጥፋው እንዴ ደግሞ» እያሉ ማጉረመረም ጀምረዋል። አይ እርስዎ ደግሞ እየተዋወቅን በሉ ይስጡኝና ምሳውም ይዘገጃጅ ብለው ወይዘሮዋ ወይ ፍንክች ያባቢላዋ ልጅ አልንቀሳቀስ አሉ። አቶ አበበ ነገሩን ለማረሳሳት ወደውጪ ወጥተው «ጎሽ ጎሽ እንዲህ ነው ልጅ በይ ሁሌም ስታጥቢ ኮቶቹን ሙሉ ለሙሉ እየፈተሽ እንድታጥቢ» ብለው ሰራተኛዋን ማሞጋገስ ቀጠሉ። ልጅት በተሰጣት ሙገሳ ተደስታ ፈገግ እያለች «ደግሞ እኮ እጄን አላስገባ ቢለኝ ሱሪውን በአንድ ወገን ገንጥዬ እኮ ነው ብሩን ያወጣሁት» ብላ ግማሽ ቀሚስ ግማሽ ሱሪ ያደረገችውን ልብስ ከአረፋው ውስጥ መዝዛ አሳየቻቸው። አቶ አበበ የሚወዱት ብቸኛ ሱሪያቸው እንዲህ ተበላሽቶ ሲያዩት ደስታቸው ሁሉ በኖ ጠፋባቸው። ምነው ምነው አንድ ሱሪዬን እንዲህ እንደ እብድ ልብስ ቀዳደድሽው ብለው ሙሾ ማውረድ እስኪቀራቸው ድረስ አለቃቀሱ።

ሱሪውን በእርጥቡ እንዳለ ተቀብለው እያገላበጡ «ምነው ብሩ ቢቀርብኝ እና አብሮ በታጠበ የጓደኛዬ ልጅ ካማሪካ ያመጣልኝ ውድ ሱሪ እኮ ነው» እያሉ ማላዘኑን ቀጠሉ። ሁኔታውን በቅርብ ርቀት ሲከታተሉ የነበሩት ወይዘሮ አሰገደች ሳቅ እየተናነቃቸው «ምንም አይደል አንድ ሺ ብር የሚያወጣ የአማሪካ ሱሪ ቢቀደድ ውስጡ 60 ብር ስለተገኘ በ15 ብር አሰፍተው እኔ እተኩስልዎታለሁ» እያሉ የለበጣ ማስተዛዘኑን ተያያዙት። አቶ አበበ ይህን ጊዜ «የ50 ሣንቲም ዶሮ የአንድ ብር ከሃምሳ ሣንቲም ገመድ ይዛ ጠፋች እንደተባለው ነው፤ በብሩ መገኘት ደስታዬን ሳልጨርስ የባሰ አመጣብኝ» ብለው አማረሩ።

ባለቤታቸውም ካረጋጉዋቸው በኋላ አግባብተው ብሩን እንዲሰጧቸው ቤት ያፈራውን ምሳ እየተመገቡ መጠየቅ ጀመሩ። «በቃ አሁን የሆነው ሆኗል 15ብሯን ይዘን ለልብሱ ማሰፊያ 30ዋን ለቡና መግዣ  የተረፈችውን 15 ብር ደግሞ ለኪስዎ ቆሎ እንኳን ቢደፉ ይዘው ወይም  ደግሞ ጠጅዎትን ይጠጡባት መቼም የደንብ ነው አይቀርም ብዬ ነው» ብለው አከፋፈለው ጨረሷት ብሯን። የዚህን ጊዜ አቶ አበበ ካፈርኩ አይመልሰኝ በሚል ስሜት የሰው የተባለችውን ብር በሂሳቡ ስሌት መሰረት ባይስማሙም 15 ብር ለባለቤታቸው ሰጥተው «ብትፈልጊ ቡና ባትፈልጊ ሻይቅጠል ገዝተሽ ጠጪበት» ብለው ወርውረውላቸው ወጡ።

አቶ አበበ ከነቁምጣቸው ናቸው፤ ሱሪያቸው ተቀዷል። በዚህ ላይ እየታጠበ ነበርና በውሃ የተነከረውን ልብሳቸውንም እንዳንጠለጠሉ ወደ ሰፈሩ ልብስ ሰፊው ዘንድ ገሰገሱ። ልብስ ሰፊው ደንግጠው ምን ሆንክ እርጥብ ሱሪ ይዘህ መጣህ ቢሏቸው ነገሩን ባጭሩ አስረዷቸው። «እናስ» አሉ ልብስ ሰፊው አቶ አበበ ግን ፈጠን ብለው ባለፈው በ70 ብር የሸጥኩልህን ሱሪ አምጣ እና ይሄን ሰፍተህ ልበስ እኔ እራቁቴን ስሄድ እብድ ከምባል አንተ የእጅ ሙያህን ተጠቅመህ ሰፍተህ መልበስ ትችላለህ። ብታተርፍ እንጂ አትከስርም ከሱሪው አንፃር ብለው እርፍ።

ልብስ ሰፊው ደግሞ እንደአጋጣሚ የለበሱት በ70 ባውንድ ከአቶ አበበ ላይ የገዙትን ቡኒ ሱሪ ነበር። እናም መረር ያለነገር ከመምጣቱ በፊት ሱሪያቸውን አውልቀው ለአቶ አበበ ሰጥተው እርጥቡን ሱሪ እስኪሰፉ እርሳቸውም በግልገል ሱሪያቸው መሃል ሰፈራቸው ላይ ከነመኪናቸው መቀመጥ ግድ ሆነባቸው። አለም የተገላቢጦሽ ናትና ከቤት በደህና ሱሪ የወጡት ልብስ ሰፊ አሁን ላይ ግማሽ እራቁታቸውን ሲቀመጡ ግማሽ እራቁታቸውን ከቤት የወጡት አቶ አበበ ደግሞ ደህና ሱሪያቸውን አድርገው መጭ አሉ።

ጌትነት ተስፋማርያም

Published in መዝናኛ
Sunday, 13 May 2018 17:32

ዳውሮ ላይ አንድ አፍታ

በዛሬው የባህል ገፃችን ወደ አንድ ስፍራ እንወስዳችኋለን። በአለም ረጅሙ የሙዚቃ መሳሪያ «ዲንካ»፣ የዱር እንስሳት እና አእዋፋት መኖሪያ ጨበራ ጩርጩራ ብሄራዊ ፓርክ፣ የአሮጌው ዓመት መሰናበቻ እና የአዲሱ ዓመት መባቻ በጣፋጮቹ «ሱልሶ እና ሲሊሶ» ብሎም እጅ በሚያስቆረጥም ቅቤ ባህላዊ ምግቦች እና በውብ ጭፈራዎች ደምቀው ወደሚያልፉበት ዳውሮ እንጓዛለን። ዳውሮ በውብ ባህል፣ በድንቅ የተፈጥሮ ስጦታ ታጅቦ፣ ተሰምቶ በማይጠገብ ታሪክ ተከቦ፤ ተዋዶ እና ተከባብሮ የመኖር እሴት የተላበሰ በደቡቧ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኝ አስደናቂ ዞን ነው።
ኢትዮጵያ የውብ ባህላዊ፣ ታሪካዊ እንዲሁም እምቅ ተፈጥሯዊ ሀብት ባለቤት እንደሆነች በተለያየ አጋጣሚ ይገለፃል። ተቆጥረው የማያልቁት ሀብቶቿ በተለያየ አጋጣሚ የሚዘረዝሩ እና አድናቆታቸውን የሚቸሩ መዛግበት፣ የተፈጥሮ ሀብት ምርምሮች እና የባህል አጥኒዎች በስፋት ቢኖሩም በአመርቂ ሁኔታ አገሪቷ ከነዚህ እምቅ ሀብቶች ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻለች የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ። በተገቢው ሁኔታ በማልማት፣ በመጠበቅ ለቀጣይ ትውልድ ከማስተላለፍ ባሻገር አገሪቷን የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን የማድረጉ ጥረትም በቂ አለመሆኑ ይነገራል። ለዚህም ይመስላል ዳውሮን የመሰሉ ድንቅ ስፍራዎች እንደ ቀልድ ልዩ ትኩረት ሳይደረግባቸው እስካሁን ድረስ የቆዩት።
በኢትዮጵያ ልዩ የባህል መስህብ፣ መንፈስን የሚያድሱ ለምለም ተፈጥሯዊ ቦታዎች፣ የጥንት አብያተ ክርስቲያናት እና መስኪዶች ብሎም የነገስታት መኖሪያ ስፍራዎች በብዛት ከሚገኙባቸው ቦታዎች መካከል የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት አንዱ ነው። ክልሉ ለአይን የማይጠገቡ፣ ታሪካቸው ቢሰማ የማይሰለቹ፣ ባህላዊ እሴቶቻቸው ተዝቀው የማያልቁ ህዝቦች መገኛ ነው።
ትንፋሽን ቀጥ አድርገው በግርምት እጅን አፍ ላይ የሚያስጭኑ ተፈጥሯዊ ስፍራዎችም በጉያው ይዟል። ሆኖም «በእጅ የያዙት ወርቅ ...» እንዲሉ እነዚህን ባህላዊ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ሀብቶችን ተንከባክቦና ጠብቆ ከቀፎ እንደሚቆረጥ ማር ለመጠቀም ሰፊ ተግዳሮቶች እንዳሉ በተለያዩ አጋጣሚ ማስተዋል ይቻላል። ከላይ ለማንሳት እንደሞከርነው በዛሬው የባህል ገፅ ዳሰሳችን በኢትዮጵያ የሚገኙ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊ እንዲሁም ታሪካዊ ሀብቶች ላይ ትኩረት አድርገናል። በተለይ ደግሞ በመግቢያችን ላይ እንዳልነው ወደ ደቡብ የአገሪቷ ክፍል በመጓዝ የዳውሮን ሀብቶች፣ ባህላዊ ስነ ስርአቶች ብሎም ኪነ ጥበባዊ ሀብቶችን እንቃኛለን። በአገሪቷ የሚገኙት ሀብቶችን በዚህ ፅሁፍ ላይ አንስቶ መዘርዘር ቀላል አለመሆኑ በመገንዘባችንም ነው ለዛሬ ዳውሮ ላይ ቆይታ አድርገን ለቀሪዎቹ ደግሞ በሌላ ጊዜ ቀጠሮ የምንይዘው።
አቶ ወንድሙ ለማ ይባላሉ። ደራሲ እና የታሪክ ተመራማሪ ናቸው። በዞኑ ባህልና ቱሪዝም እና መንግስት ኮሙኒኬሽ ጉዳዮች መምሪያ የባህል ታሪክ እና ቅርስ ጥናት እና ልማት ዋና የስራ ሂደት ባለቤት ናቸው። በጋሞ ጎፋ ዞን በአርባ ምንጭ ከተማ በተካሄደው ሶስተኛው የደቡብ ክልል ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ፌስቲቫል እና አውደ ርዕይ ላይ ተገናኝተን ስለ ዳውሮ ሀብቶች እንዲህ ተጨዋወትን። ዞኑን ወክለው የመጡ የባህል ቡድኖች ዳውሮን በስፍራው የተገኘን ያህል በድንቅ ትወናቸው አስመለከቱን። የተፈጥሮ ስፍራዎቿን፣ ጭፈራዋን፣ ባህል እና ወጓን የሙዚቃ መሳሪያዎቿን ተጠቅመው እዛው ዳውሮ ወስደው መንፈሳችንን አደሱት።
ዳውሮን በወፍ በረር
ደቡብ ምዕራብ። ወደ ስፍራው ሲሄዱ በእርግጠኝነት ከከተሜነት ጋር ይኳረፋሉ። የእስከ ዛሬው ኑሮዎት ከተፈጥሮ ጋር የተኳረፈ ይመስሎታል። ጥቅጥቅ ደኖች ልዩ ተፈጥሯዊ ሀብቶች ለደቡብ ምእራብ ያለስስት ተችሯታል። በዚያ ላይ ደግሞ በውብ ባህላቸው ተከባብረው የሚኖሩ ብሄረሰቦች እነዚህን ውብ ስፍራዎች እንደ አይናቸው ብሌን ጠብቀው አቆይተዋቸዋል። በዚህ ስፍራ ነው እንግዲህ የዳውሮ ህዝብ የሚገኘው። የወጀብ እና ኦሞ ዞን ደግሞ ይህን ውብ ስፍራ መሀል አድርገው ቁልቁል ይፈሳሉ።
«ዳውሮ ላይ ድንገት አዳልጦህ ብትወድቅ ልትደነግጥ አይገባም። ምክንያቱም ቅቤ ላይ ነው ምትወድቀው» በማለት በፈገግታ ተሞልተው ስፍራው በንፁህ የቅቤ ምርቱ የሚታወቅ መሆኑን የባህል ታሪክ እና ቅርስ ጥናት ተመራማሪው አቶ ወንድሙ ይናገራሉ። ከዚህም ሌላ እጅግ ብዙ የሚነገሩ እሴቶች እንዳሉትም ያስረዳሉ።
ባህላዊ እና ታሪካዊ እሴቶች
ዳውሮ አምስት ወረዳዎች አሏት። ተርጫሰ የዞኑ ከተማ ነች። በአንድ እረድፍ 175 ኪሎ ሜትር በአማካኝ በሰባት እረድፍ ደግሞ 1225 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው፣ ከ2ነጥብ 5 እስከ 3ነጥብ 8 ከፍታ ብሎም ከ2 ሜትር እስከ 5 ሜትር ስፋት ያለው የንጉስ አልሀላ የድንጋይ ካብ በዚህ ስፍራ ይገኛል። የጎጀብ እና ኦሞ ወንዞችን ታክኮ የተገነባው ይህ ካብ በጥንታዊነቱ እና በታሪክ መዝገብ ላይ ባለው ትልቅ ቦታ ምክንያት የቱሪስት መዳረሻ ሊሆን የሚችል አስደናቂ ስፍራ ነው። ይህ ስፍራ 1ሺ870 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው የግቤ ሶስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ በስፍራው መገንባቱን ተከትሎም የተፈጠረ ሰው ሰራሽ ሀይቅ አለው። ይህ ደግሞ ከታሪካዊው ስፍራ ጋር ተዳምሮ ዳውሮን ልዩ የውበት ካባ ደርቦላታል።
በሀይቁ ላይ በጀልባ የሚንሸራሸር ሁሉ የንጉሱን የድንጋይ ካብ መጎብኘት ይችላል። የንጉስ አልሀላ ታላቁ ቤተ መንግስት በሶስት ስፍራዎች ይገኛል። የመጀመሪያው በሎማ ወረዳ ሲሆን፤ ሁለተኛው በኮይሻ ቀበሌ ይገኛል። ሶስተኛው ደግሞ በቶጫ ወረዳ ነው የሚገኘው። ጥንታዊት ዳውሮ ከ1532 ዓ.ም እስከ 1889 ዓ.ም ለማዕከላዊ መንግስት ሳትገብር እራሷን አስተዳድራለች። ሌላኛው ደግሞ የ« ኩይላ ኮንዲያ የመካነ መቃብር ስፍራ በዞኑ ይገኛል። ከንጉስ አፄ ናውድ አገዛዝ ጀምሮ በዞኑ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት አሉ። ከዚህ ውጪ በዳውሮ «የተፈጥሮ ሆስፒታሎች» ተብለው የሚጠሩ ፍል ውሀዎች ይገኛሉ።
የዳውሮ ህዝብ እንግዳ ተቀባይ፣ የልዩ ልዩ ባህላዊ እሴቶች ባለቤት ነው።
አቶ ወንድሙ ስለ ዞኑ ነዋሪዎች ሲናገሩ «ህብረተሰቡ ግማሽ መንገድ ድረስ በመሄድ እንግዶቹን የሚቀበል የድንቅ ስብእና ባለቤት ነው» በማለት ነው። ባህላዊው እርሻና እንክብካቤ፣ የእንሰት ተክል እና አጥር የዳውሮ ልዩ መገለጫዎች ናቸው። የጨበራ ጩርጩራ ብሄራዊ ፓርክ በ119ሺ ሄክታር መሬት ላይ ተከልሏል። በዳውሮ ዞን እና በኮንታ ልዩ ዞን መካከል ይገኛል። በፓርኩ ውስጥ ዝርያቸው እየጠፋ የሚገኙ የአፍሪካ ዝሆን፣ ጎሽ፣አንበሳ፣ ነብር እንዲሁም የተለያዩ የዱር እንስሳት እና አእዋፋት ይገኙበታል። ተፈጥሯዊ ልምላሜውም እጅግ አስደናቂ ነው። ዳውሮ ላይ አትርፎ እንጂ ከስሮ የሚመለስ የለም።
የአንገለቲ ጋቢ የፍርድ ችሎት
ከ1829ዓ.ም ጀምሮ ለ40 ተከታታይ ዓመታት የመራው የዳውሮው ንጉስ ዳጎዬ በነበረበት ዘመን በቶጫ ወረዳ ዶቶሬ በሚባል አካባቢ ባህላዊ የዳኝነት ችሎት ከፍታ መክፈቷ ይነገራል። ይህ ባህላዊ ዳኝነት «ክፍት» ወይም «all court hearings shall be open to the public» ስለ ፍርድ ሂደቱ ማወቅ የሚፈልግ ማንም ሰው እንዲገኝ እና እንዲከታተል ታደርግ ነበር። በዚህም ሜዳ ላይ በሚደረግ የፍርድ ስርዓት ሁለት የፍርድ መስጫ ችሎቶችን በማዘጋጀት ንግስቲቱ እራሷ ፍትህ ለተነፈገ ፍትህን በደል ላደረሰ ተገቢውን ቅጣት ትሰጥ ነበር።
ንግስቲቱ ይህን ባህላዊ የፍርድ ስርአት በመዘርጋት የዳውሮ ህብረተሰብ ፍትህ እንዲያገኝ ከማድረጓም በላይ ሰዎች በሙግት እና ግጭት የሚያጠፉትን ጊዜ ለስራ እንዲያውሉት ታደርግ ነበር። ለ40 አመታት ፍርድ ሲሰጥበት የቆየው ችሎትም እስካሁን ድረስ በዳውሮ ዞን በታሪካዊነቱ የሚጠቀስ እና ስፍራው እንዳይጠፋ ተከልሎ የሚጠበቅ ነው።
ባህላዊ ሙዚቃ እና እደ ጥበብ
ዳውሮ «በዲንካ» የሙዚቃ መሳሪያ ባንድ ይታወቃል። አጥኚዎች እና የታሪክ ተመራማሪዎች እንደሚጠቁሙት ዘመናዊ ባንድ በአገር ፍቅር፣ በማዘጋጃ፣ በብሄራዊ ቴአትር ቤቶች ከመቋቋሙ በፊት የብሄረሰቡ መገለጫ የሆነ የሙዚቃ መሳሪያ ባንድ ነው። ዲንካ የባንድ መጠሪያን የወሰደበት ምክንያት አምስት የትንፋሽ እና አንድ የከበሮ ወይም ዳርቢያ ሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾችን በአንድነት በመያዙ ነው። ዲንካ ከ8 በላይ ቅኝቶች ሲኖሩት ዳርቢያ የሚጫወተው የቡድን መሪ በመሆን ጓደኞቹ ቅኝት እየቀያየሩ እንዲጫወቱ ያደርጋል። የትንፋሽ መሳሪያዎቹ ዞሃ፣ ላሚያ፣ኦይቲሲያ፣ሄሲያ እና ማራ ከ3ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ቀርክሀ በመጠቀም ጫፉ ላይ የአጋዘን፣ የበሬ ቀንድ እንዲሁም የፍየል ቀንድ በማስገባት የሚሰራ ነው።
ዲንካ ባለ ከረባቱ የሙዚቃ መሳሪያ እየተባለ ይጠራል። በርዝመቱም ቢሆንም በአለም ላይ ተወዳዳሪ የሌለው ነው። ማህበረሰቡ ይህን ሙዚቃ ቀለብን ከሚገዛ ባህላዊ ውዝዋዜ ጋር ሲጫወቱት ማድመጥ እና መመልከት እጅግ መሳጭ እና የማይሰለች ውበ ጊዜን ለማሳለፍ የሚመረጥ የመንፈስ ምግበ እንደማግኘት ነው። በጥንታዊት ዳውሮ ዲንካ ንጉሱን በተለያዩ ክብረ በዓላት ለማጀብ የሚጠቀሙበት ነበር።
ማንቻላ
ማንቻላ የዳውሮ ባህላዊ የቆዳ ምንጣፍ ነው። ይሄ ከቆዳ የተሰራው ምንጣፍ በተለያየ መንገድ በማለስለስ እንደ ወረቀት ለተለያዩ የስነ ፅሁፍ አገልግሎቶች ይውል ነበር። በጥንታዊ ዳውሮም ታሪካዊ እና ስነ ፅሁፋዊ እሴቶችን ከተፈጥሮ እፅዋት በተሰሩ ቀለማት በመፃፍ ለትውልድ የማስተላለፍ እና ጠብቆ የማቆየት ስራ ይከናወን ነበር።
ዳውሮን በአጭሩ ዳስሶ መጨረስ እጅግ ከባድ ነው። እምቅ ባህላዊ ሀብቶች ያላት እና በተፈጥሮ ፀጋ የታደለች ስፍራ ናት። ከዚህ ውስጥ አገረሰባዊ የእደ ጥበብ ውጤቶቿ በዋናነት ይጠቀሳሉ። የዳውሮ ብሄረሰብ ባህላዊ አልባሳት ማዳማሻ፣ ዱንጉዛ ሀዲያና ዳዋሊያ ዳንጩዋ፣ ዋሩዋ ቡሉኩዋ ተወዳጅ እና ማንነትዋን ፍንትው አድርገው የሚገልፁ ናቸው። ጥንታዊነታቸው እና የጥለት አጣጣል ዲዛይናቸው ለአይን ማራኪ እና ውበትን የሚያጎናፅፉ ናቸው። ዘመናዊው የግብይት ስርአት ተዘርግቶ ገንዘብ ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት ፈትል ወይም በጥጥ የሚሰሩ ሻልዋ ለመገበያያነት ይውል ነበር።
ዳውሮ በባህላዊ መንገድ ከአፈር ውስጥ ብረት በማውጣት ያመረታል። በተለይ አዳ በቾ፣ አንቀለ በቾ፣ ሾታ፣ ጩርጩራ፣ ቦላ ጡማ፣ ዎጣ ሴሎ፣ ጋልዳ ግርጫ እንዲሁም መንቃላ በሚባሉ አካባቢዎች ብረትን ከአፈር ውስጥ በማምረት ቅርፅ በማውጣት ለተለያዩ የእርሻ መሳሪያዎች እና ለቤት ውስጥ ቁሳቁሶች ጥቅም ላይ እንዲውል ያደርጋሉ።
«ከቻይና ተመርቶ ከሚመጣው ቢላ በተሻለ በዳውሮ የሚመረተው ቢላ ጥራት ያለው ነው›› የሚሉት የቅርስ ጥናት ተመራማሪው አቶ ወንድሙ እርሳቸው ከመወለዳቸው በፊት አባታቸው ከእናታቸው ጋር ጋብቻ ሲፈፅሙ የነበረ ቢላዋ እስካሁንም ድረስ በቤታቸው አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ይናገራሉ። ይህ መሳሪያ በባህላዊ መንገድ የዳውሮ ማህበረሰብ ብረት በማምረት ቅርፅ አውጥቶ የሰራው ነው። በዳውሮ ጥራት ያለው ብረት ለማምረት የሚያስችል እምቅ ተፈጥሯዊ ሀብት አለ።
እንደ መውጫ
ዳውሮን መጎብኘት ብዙ መማር ነው። ብዝሀነትን የሚያከብር፣ ተፈጥሮን እና ታሪክን ጠብቆ የማቆየት ባህል ያለው የአንድነት ተምሳሌት መሆን የሚችል ዞን ነው። በዚህ አካባቢ በርካታ የአገር በቀል እውቀት አለ። ቅን ህዝብ ታሪኩን እና አገሩን የሚወድ ህበረተሰብም አላት ዳውሮ። የታሪክ፣ የባህል የተፈጥሮ ተመራማሪዎች የማህበረሰቡን እሴቶች በቦታው ላይ በመገኘት የማጥናት ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባል። የክልሉ እና የፌደራል ባህልና ቱሪዝም መስሪያ ቤቶች ቀጥተኛ ኃላፊነት በመውሰድ የዳውሮ ሀብት እንዲለማ፣ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን ሊሰሩ ይገባል። አለም የተቸገረበት እና መድሀኒት ያጣበት በሽታ በዳውሮ ሊፈወስ ይችላል። ማን ያውቃል? ለዚህ ግን የህክምና ባለሙያዎች የዳውሮ አባቶች የሚቀምሟቸውን ባህላዊ መድሀኒቶች በስፍራው በመገኘት መመርመር እና ማጥናት ይኖርባቸዋል።
ስለ ዳውሮ ውብ ባህል ማራኪ ተፈጥሮ እና ታሪክ እያወሩ መቆየት ምርጫችን ቢሆንም አንድ ቦታ መቆም የግድ ይለናል። በሌላ ጊዜ ታሪካዊ በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በብሄራዊ ቅርስነት ተመዝግበው እውቅና የተሰጣቸውን የዳውሮን ጉስካዎ ሀላላ የድንጋይ ካቦች ቦታው ድረስ በመገኘት ጉብኝት አድርገን ዳሰሳውን ይዘንላችሁ እንቀርባለን። ሰላም!

ዳግም ከበደ 

Published in ማህበራዊ

ሥዕል የጥበብ መጀመሪያ ነው ማለት እንችላለን። ምክንያታችን ደግሞ ወደ ጥንታዊ የሰው ልጅ የጥበብ አጀማመር ይወስደናል። በብዙ የሰው ልጅ ታሪኮች ውስጥ የዋሻ ውስጥ ኑሮ እንደ መነሻ ሲደረግ በታሪክ ድርሳናት ላይ የምናየው ነው። የሥዕል ጥበብም በሰው ልጅ የዋሻ ውስጥ ኑሮ ይጀምራል።
የሰው ልጅ አሁን ያለበትን ዓለም ከመኖሩ በፊት በዋሻ ውስጥ እያለ ነው የዚህን ረቂቅ የቴክኖሎጂ ዘመን ጥበብ የጀመረው፡፡ በድንጋይ ላይ የቅርጻቅርጽ አይነቶችን ይስላል፡፡ ቤት ሰርቶ ከመኖሩ በፊት የቤትን ቅርጽ በሥዕል ያሳያል። እንስሳትን ከማላመዱ በፊት እንስሳትን በሥዕል ይሰራ ነበር። በሥዕል የጀመራቸውን ነገሮች በኋላ ወደ እውነተኛ ነገር አመጣቸው።
እንዲያውም እዚህ ላይ አንድ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ሀሳብ ትዝ አለኝ። ዶክተር ዓብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሳሉ የተናገሩት ነበር። የንባብ ለሕይወት ፕሮግራም ነበር። የመክፈቻ ስነ ሥርዓቱ ላይ የወቅቱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር የአሁኑ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ንግግር እንዲያ ደርጉ ተጋበዙ።
ይህ ታዳሚውን ያስደመመ ንግግራቸው ደግሞ ስለሥዕል የጀመርኩትን ሀሳብ የሚያጠናክርልኝ ሆኖ ስላገኘሁት ሀሳቡን ላጋራችሁ። ዶክተር ዓብይ እንዳሉት፤ የሰው ልጅ ከሚጨበጥ የፈጠራ ሥራ በፊት የሚሰራው የማሰብና የመፍጠር ሥራ ነው። ሳይታሰብ የሚሰራ ምንም ነገር አይኖርም። የሰው ልጅ እሳትን ከመፍጠሩ በፊት እሳት የሚባል ነገር መኖር እንዳለበት አስቦ ነው። ያሰበውን ነገር በሥዕል ወይም በሌላ የጥበብ ዓይነት ይጀምረዋል። ባሰበው ልክ ደግሞ ወደ እውነተኛ ነገር ያመጣዋል። ደራሲዎች ወደፊት መሆን ያለበትን ነገር ያስባሉ፤ ይተነብያሉ። ለአብነት ‹‹ራይት ብራዘርስ›› ወይም በአማርኛችን ሁለቱ ወንድማማቾች አውሮፕላን ፈጥረዋል። ‹‹ሁለቱ ወንድማማቾች አውሮፕላንን ከመፍጠራቸው በፊት አንድ የግሪክ ደራሲ ስለአውሮፕላን ጽፎ ነበር›› ይላሉ ዶክተር ዓብይ። መጀመሪያ እሳቤው ይመጣል፤ ንድፈ ሀሳቡ ይሰራል። ከዚያ ነው ሌሎቹ የሚከተሉት። በመሆኑም አሁን የሚታዩት አስደናቂ የቴክኖሎጂ ምርቶች መጀመሪ ያቸው በንድፍ ደረጃ ታስበው ነው።
የዶክተር ዓብይ ሀሳብ ብዙ እውነት ያሳየናል። ለምሳሌ የሕንጻ አሰራር ዲዛይን እንውሰድ። የሕንጻው ግንባታ መሬት ላይ ከመሰራቱ በፊት መጀመሪያ ረቂቁ የሚሰራው በወረቀት ነው። ስለዚህም መጀመሪያ የሚያስፈልገው የሕንጻው ቁሳቁስ ብሎኬት፣ ብረታብረትና ማሽን ሳይሆን እርሳስ፣ ማስመሪያና ወረቀት ይሆናል። ከዚያ በኋላ ነው ብሎኬት የሚያስፈልገው።
ሥዕል ከሰው ልጅ ሕይወት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ስለሆነ የጥበብ መጀመሪያ ልንለው እንችላለን። በዚያ ላይ ሥዕል ከሌሎች የጥበብ አይነቶች ሁሉ ልዩ ችሎታ የሚጠይቅ ነው። እንዲያውም እኮ ‹‹አርት›› የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል የሚያገለግለው ለቅርጻቅርጽ ጥበብ ነው። በዚሁ ይቀጥልና እንግሊዘኛው የቅርጻቅርጽ ጥበብን ‹‹አርክቴክት›› ይለዋል። ‹‹አርት›› የሚለው ሥዕል ላይ ያተኩራል። አርቲስት የሚባለውም ለሠዓሊ ነው።

በነገራችን ላይ ወደ አማርኛው ስንመጣ ብዙ የተምታታ ነገር አለ። ኪነ ጥበብና ስነ ጥበብን በተለያየ መልኩ የመጠቀሙ ሁኔታ መኖሩን ብቻ መመልከት ይበቃል። አንዳንዶች ስነ ጥበብ ለሥዕልና ለቅርጻቅርጽ የጥበብ ሥራዎች ሲሆን፤ ኪነ ጥበብ ደግሞ እንደ ፊልም፣ ሙዚቃ፣ ድርሰት ያሉትን የሚይዝ ነው ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ሁለቱም ልዩነት እንደሌላቸው ያስቀምጣሉ። ለዚህም ነው ብዙ ቦታ ተደበላልቆ የምናየው።
በግልጽ የሚታየው ነገር ደግሞ ደራሲውም፣ ተዋናዩም፣ ዘፋኙም፣ ገጣሚውም፣ ‹‹አርቲስት›› ተብሎ ይጠራል። «አርቲስት» የሚለው ‹‹አርት›› ከሚለው የእንግሊዘኛው ቃል የመጣ ነው፡፡ የእንግሊዘኛው አርት ደግሞ ለሥዕልና ቅርጻቅርጽ ጥበብ ያገለግላል። ስለዚህም ‹‹አርቲስት›› የሚለው ቃል ለሠዓሊ ብቻ የሚሆን ነው ብለው የሚከራከሩ ወገኖች አሉ።
የስያሜው ነገር ይቅርና ራሱ ወደ ሥዕል ስንመለስ የጥበብ መጀመሪያ እንደመሆኑ ትኩረት በማጣት የጥበብ መጨረሻ ሆኗል። ዘወትር ከምናስተውላቸው ነገሮች ተነስተን ማየት እንችላለን፡፡ አንድ የሙዚቃ ኮንሰርት ቢዘጋጅ ከፍተኛ ገንዘብ ተከፍሎ ይገባል፤ ለዚያውም በረጅም ቀን ወረፋ ተይዞ፡፡
የግጥም መድረክ ሲዘጋጅ አዳራሽ ሙሉ ሰው ይገኛል። የመጻሕፍት ሽያጭና ዓውደ ርዕይ ላይም ቢሆን እንደ ሙዚቃ ባይሆንም ከሥዕል የተሻለ ታዳሚ ይገኛል። የሥዕል ዓውደ ርዕይ ሲዘጋጅ ልብ ብላችሁ ታውቃላችሁ? መግቢያ በነጻ ሆኖ አሥር እንኳን የሚደርስ ታዳሚ ላይኖር ይችላል።
ሥዕል የሌሎች የጥበብ ሥራዎችን ያህል ለምን ትኩረት አላገኘም? ብለን ብንጠይቅ አንድ ወጥ ምላሽ አናገኝ ይሆናል። ዳሩ ግን አንዳንድ ምክንያቶች ደግሞ ይኖራሉ። በጥበብ ቅርጻቅርጽ ሙያ ውስጥ ያሉ ሰዎች ለሥዕል ጥበብ ትኩረት እንዳልተሰጠው፣ በመንግሥትም ምቹ ሁኔታዎች እንዳልተፈጠሩለት ይናገራሉ።
ወጣት አወቀ ዓለሙ ይባላል። የቴአትር ተመራቂ ሲሆን የሥዕል ባለሙያም ነው፡፡ ‹‹ሰዓሊ ተብሎ ለመጠራት ገና ይቀረኛል›› ስላለኝ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ወጣት እያልኩ ለመጠቀም ተገድጃለሁ። ወጣት አወቀ እንደሚለው፤ ለሥዕል ጥበብ ማንም ትኩረት አልሰጠውም። በመንግሥት ደረጃም ቢሆን ለሌሎች የኪነ ጥበብ ሥራዎች የሚሰጠውን ያህል ድጋፍ አያገኝም። አንድ ሰዓሊ ዕድሜውን ሙሉ ሥዕል ሲሰራ ኖሮ አንድ ነጠላ ዜማ የለቀቀ ሰው ያህል የሚያገኘው ነገር የለውም፤ ሥዕልን ለሽያጭ የሚያበቃ ነገር የለም።
በሌላ በኩል ደግሞ ከህዝቡም ያለው ከበሬታ የዘፋኝን ያህል እንደማይሆን ታዝቧል። አንድ ዘፋኝ ወይም ተዋናይ በአንድ ሥራ ብቻ ዝነኛ ይሆናል፤ ዝነኛ ሲሆን ደግሞ ሥራዎቹ ምንም ይሁኑ ምን ይሸጡለታል። ሠዓሊ ግን ይህን ዕድል ማግኘት አይችልም። የመገናኛ ብዙኃንን ሽፋን በተመለከተም ሥዕል ላይ ከፍተኛ ክፍተት እንዳለባቸው ነው ወጣት አወቀ የሚናገረው። አንድ ዘፋኝ ወይም ተዋናይ በብዙ መገናኛ ብዙኃን ተደጋግሞ እንግዳ ይደረጋል፤ በአንድ መገናኛ ብዙኃን እንኳን ተደጋግሞ ይቀርባል።
ስለሠዓሊ ሥራዎች ግን አያወሩም። በአገሪቱ ውስጥ ብዙ ሠዓሊዎች አሉ፤ ግን ማንም አያውቃቸውም። ምክንያቱም መገናኛ ብዙኃን አላስተዋወቋቸውም፤ ሥራዎቻቸውም አልታዩም። የቴክኖሎጂ መስፋፋትና አስደናቂነትም ሌላው የሥዕል ተግዳሮት ሊሆን እንደሚችል ወጣት አወቀ ይጠቅሳል። የተለያየ አስደናቂና ጥራት ያላቸው የፎቶ ዓይነቶች መምጣታቸው ሰዎች ወደ ሥዕል እንዳያተኩሩ ያደርጋል። በቀላሉ ስልካቸው ላይ ብዙ ነገሮችን ያያሉ። ይህ ይሁን እንጂ ሥዕልና ፎቶ ፈጽሞ እንደማይገናኝ ነው አወቀ የሚናገረው።
ሥዕል ጥበብ ነው፤ ፎቶ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ቴክኖሎጂ የሰው ልጅ ጥበብ ቢሆንም ሥዕል ደግሞ ቀጥተኛ የሆነ የጥበብ ሥራ ነው፤ ፎቶ ግን በቴክኖሎጂ መሳሪያዎች የተነሳ ውብ ሆነው ሊታዩ ይችላሉ። ፎቶ ማንም በመለማመድ ሊያነሳ ይችላል፤ ሥዕል ግን ተሰጥዖን ይጠይቃል። በፎቶ ውስጥ ጥበብ አለ፤ ፎቶ የሚያነሳ ሰው ብዙ ጥበብ ይጠቀማል፤ ይሁን እንጂ ሥዕልና ፎቶ ላይ ያለው ጥበብ በጣም የተራራቀ ነው።
ሥዕል ለሰዓሊው የውስጥ ስሜት ጭምር ነው። ፎቶ በቁስ አካል ላይ ብቻ የተገደበ ነው። ህልምን ፎቶ ማንሳት አይቻልም። ሠዓሊ ግን ህልሙን መሳል ይችላል። ሥዕል በቁስ አካልና በተፈጥሮ ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም። ረቂቅ የሰው ልጅ የውስጥ ስሜት ነው። በሌላ በኩል ሥዕል ላይ ያለውን ነገር ፎቶ ላይ ማግኘት አይቻልም፤ ለምሳሌ የጥንት ሥራዎችን ሥዕል ላይ እንጂ በፎቶ ማግኘት አይቻልም። ሥዕል ባህል ነው፤ ታሪክ ነው። በየዘመኑ የነበረውን ሁነት ያሳያል።
ሥዕል እንደ ሌሎች የኪነ ጥበብ ሥራዎች የታዳሚ ጋጋታ ያላገኘበት ሌላም ምክንያት ይኖራል። ይሄውም ሥዕል እንደ ሙዚቃ ለሁሉ ግልጽ አይደለም፡፡ እንደ ፊልም ለማንም ቶሎ የሚገባ አይደለም። ተደጋግሞ እንደሚባለው ሥዕል ረቂቅ ነው። የሚረዳው የተወሰነ ሰው ሊሆን ይችላል። ሥዕል ለሠዓሊው ብቻ ሳይሆን ለተመልካቹም ጥበብ የሚጠይቅ ነው። እርግጥ ነው ሥዕል የሚወድ መሣል የሚችል ብቻ ነው ማለት አይደለም፤ ግን ሥዕልን መውደድና መረዳት ራሱን የቻለ ጥበብ ነው። ለዚህም ነው በሥዕል ዓውደ ርዕይ ላይ በጣም ጥቂት ሰዎችን ብቻ የምናገኘው።
በዚህ የሥዕል ረቂቅነት ላይ ነው እንግዲህ አንድ አከራካሪ ሀሳብ የሚነሳው። ይሄውም ሥዕል ማብራሪያ ያስፈልገዋል አያስፈልገውም የሚለው ነው። በእርግጥ ጥበብ እንደጥበብነቱ ራሱን የሚገልጽ መሆን አለበት። ማብራሪያ ሳያስፈልገው ሥዕሉ በራሱ የሚሰጠው ትርጉም ነው ጥበብ መሆን ያለበት። የሥዕል ባለሙያዎችም የሚሉት ይህንኑ ነው። ሥዕል ማብራሪያ ሳያስፈልገው ራሱ የሚሰጠው ትርጉም ጥበብ ነው። ምክንያቱም ‹‹ይሄ እንዲህ ነው፣ እንዲህ ለማለት ተፈልጎ ነው፣ ይህን በእንዲህ ተረዱት…›› ማለት ጥበብ ሳይሆን የሰዎችን የመረዳት አቅም ማዳከም ነው።
ከተመልካቾች ደግሞ የዚህ ተቃራኒ ሀሳብ ይነሳል። ሥዕልን ማንም በግልጽ ሊረዳው አይች ልም፤ ስለዚህ ማብራሪያ ያስፈል ገዋል የሚሉ አሉ። ይህን አስተያየት ከሚሰጡ አንዱ አብዱ ከድር ይባላል። አብዱ እንደሚ ለው፤ ሠዓሊው በሰራው የሥዕል ሥራ ላይ ገለጻ ማድረ ግመቻ ል አለበት ።ይህም ሰዎ ችን ሥዕልን እንዲ ያዩ ያደርጋል። የገባው ብቻ ይየው ብሎ ማስቀመጥ ሥዕሉን እንዳይታይ ማድረግ ነው። ምንም እንኳን ሠዓሊው የሳለበት ስሜትና ተመልካች የሚረ ዳበት የተለያየ ሊሆን ቢችልም ምን አስቦ እንደሰ ራው ገለጻ ማድረግ ይገባ ዋል። ሥዕሉ ሊሸጥም ሆነ ብዙ ተመል ካች ሊያገኝ የሚችለው ሰዓሊው ገለጻ እያደረገበት ከሆነ ነው።
ሠዓሊና የቅርጻቅርጽ
ባለሙያ የሆነው ተስፋ ሁን ክብሩ በበኩሉ፤ ሥዕል በራሱ ነው መናገር ያለበት፤ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ሰዎች ሥዕልን እንደ ጥበብ ስለማያዩት መተርጎም ያስፈልገዋል። ለዚህ ነው እንኳን ሰዓሊ ተመልካች የጠፋው። አንድ ተማሪ ከልጅነቱ የሥዕል ችሎታ ቢኖረው እንኳን ያለፍላጎቱ ነው ሌላ ነገር የሚጫንበት። ሥዕልን ሙያዬ ብሎ መያዝም አይችልም።
እንደ ተስፋሁን ሀሳብ ከሆነ፤ ተማሪዎች መዋዕለ ሕጻናት ውስጥ እያሉ የደረጃ ውድድር መኖር አልነበረበትም፤ በነጻነት ችሎታቸውን ማወቅ ነው ያለባቸው። የሥዕል ጥበብ፣ የሙዚቃ ችሎታ፣ የገጣሚነት ተሰጥዖ ያለው ሕጻን የግድ በሂሳብ ብቻ እንዲወዳደር ከተደረገ ገና ከሕጻንነቱ ጫና እየተደረገበት ነው።በተፈጥሮ የተሰጠውን ችሎታ አያውቀውም፤ ቢያውቀውም ምንም እንደማይጠቅም ይረዳል። ምክንያቱም ውድድሩ በሌሎች ትምህርቶች ብቻ ነው። ይህ ነገር ከሕጻናት ላይ መውረድ እንዳለበት ያሳስባል። ይህ ከሆነ ነው ጥበብን የመረዳትም ሆነ የመሥራት ችሎታ የሚኖረው ይላልም።
የኢትዮጵያ ሠዓሊያንና ቀራፂያን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ሥዩም አያሌው ማህበረሰቡ ለሥዕል የሚሰጠው ትኩረት ላይ ትዝብት አላቸው። እንዲያውም አንድ በቴሌቪዥን የተላለፈ የትምህርት ማስታወቂያ ላይ እንደታዘቡት፤ ተማሪው ትምህርት አይከታተልም ተብሎ ለአባቱ ይሰጣል። አባቱም እየተቆጣጠረው እንደሆነ ይናገራል። በኋላ ለአባትየው የልጁን ደብተር አሳዩት። ደብተሩ ሲታይ ሥዕል ነው የሚሞነጫጭርበት፤ የዚህን ጊዜ አባትየው በጣም አዘነ። ሥዕል መሳል የሰነፍ ተማሪ ሥራ ሆነ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ሥዕል የሰነፍ ተማሪ አይደለም፤ እንዲያውም የተለየ ጥበብና ችሎታ የሚጠይቅ ነው።
እዚህ ላይ የተስፋሁን ክብሩን ሀሳብ ደግመን እናንሳው። ‹‹ተማሪዎች ሂሳብና ሌላው ትምህርት በግድ ይጫንባቸዋል›› ብሏል። ሌላ አስታራቂ ሀሳብ ብናነሳስ? ተማሪዎች ሒሳቡንም ሆነ ሌላውን ትምህርት ይማሩ፤ የፊዚክስ ተመራማሪ ሆኖ እኮ ሠዓሊ መሆን ይቻላል። ሠዓሊ መሆን የኬሚስትሪ ተመራማሪ ከመሆን አያግድም። ስለዚህ የሥዕል ችሎታ ያለውን ሰው ሌላውን ትምህርት እንዳይማር ከማድረግ እየተማረ ሥዕል ቢስልስ? እንዲያውም ሥዕል ተሰጥዖ ስለሆነ ከትምህርት ሠዓት ውጭ መንፈሱን የሚያድስበት ሊሆን ይችላል። ሒሳብ እያጠና ሁሉ እኮ ሥዕል ሊሰራ ይችላል፤ ሀሳብ ሊመጣለት ይችላል።
እዚህ ላይ ትልቁ ስህተት ይልቅ ወላጆች ሥዕልን የሰነፍ ምልክት የሚያደርጉት ከሆነ ነው። እንዲያውም እኮ በተለይም የፊዚክስና የሒሳብ ትምህርቶች ከቅርጻ ቅርጽ ጋር የተያያዙ ናቸው። እዚህ ላይ አንድ ማሳያ ብናነሳስ? በትምህርት ቤት ውስጥ የሒሳብና የፊዚክስ ትምህርት ላይ ቅርጻቅርጽ መሥራት የማይችሉ ተማሪዎች ስሩልን እያሉ ሲለምኑ ይታያል። ሰለዚህ አለመቻላቸው አስቸገራቸው ማለት አይደለ? በተለይም የጂኦሜትሪ ትምህርት ላይ ብዙ ተማሪዎች ይቸገራሉ።
ጂኦሜትሪ አለመቻል ደግሞ አንዱ የሒሳብ ትምህርት ዘርፍ ነውና ሒሳብ አለመቻላቸውን ያሳያል። በተመሳሳይ የ11ና የ12ኛ ክፍል የሳይንስ ተማሪዎች ድሮይንግ ተብሎ ትምህርት ይሰጣቸዋል። ታዲያ የሥዕል ችሎታቸውን እያዳበሩ ካልመጡ በምን መልኩ ነው ውጤታማ ተማሪ ሊሆኑ የሚችሉት? መልሱን ለአንባቢዬ ልተወው።
የሥዕልን ረቂቅነት በተመለከተ የሥዕል ባለሙያው ወጣት አወቀ ዓለሙ በሰጠን አስተያየት ሀሳባችንን እናጠቃለው። አንድ ሥዕል ማብራሪያ ያስፈልገዋል አያስፈልገውም የሚባለው እንደ ሥዕሉ ባህሪ ነው። አንዳንዱ ሥዕል ለማንም ግልጽ ሊሆን ይችላል፤ አንዳንዱ ደግሞ በጣም ረቂቅ ይሆናል። በጣም ረቂቅነቱ የጎላና ለመረዳት እስከሚያስቸግር ከሆነ ሠዓሊው ማብራራት አለበት እንጂ ካልተረዱት ይተውት አይባልም፤ ወይ ማስረዳት አለበት ወይም ሥዕሉ ግልጽ ሊሆን ይገባል።
የሥዕል ትርጓሜ ጥበባዊነት ‹‹ጥበብ ለጥበብ እና ጥበብ ለዓላማ›› የሚባል ነገር እንዳለም አወቀ ይናገራል። ጥበብ ለጥበብ የሚባለው መግለጫ አያስፈልገውም፤ ሠዓሊውም የሳለው ስሜቱን እንዲገልጽለት ነው። ጥበብ ለዓላማ የሚባለው ደግሞ ሥዕሉ የሚሳለው ዓላማ ተኮር ሆኖ ነው። ሀሳብን ለመናገር፣ መልዕክት ለማስተላለፍ ወዘተ ሊሆን ይችላል። ስለዚህም በሥዕሉ መልዕክት ለማስተላለፍ ከሆነ ማስረዳት ያስፈልግ ይሆናል፤ ወይም ሥዕሉ በራሱ ግልጽ መሆን አለበት።
በሌላ በኩል ሠዓሊው የሳለበት ስሜትና ተመልካቹ የሚረዳበት ስሜት የተለያየ ቢሆን ይህም የጥበብ ባህሪ ነው። ተመልካቹም የራሱ ትርጉም ሊሰጠው ይችላል፤ የግድ ከሠዓሊው ሀሳብ ጋር መመሳሰል አለበት ተብሎ አይወሰድም። ይህ በሥዕል ብቻ ሳይሆን በሌሎች የጥበብ ሥራዎች ላይም የሚታይ የራሱ የጥበብ ባህሪ ነው።

ዋለልኝ አየለ

Published in ማህበራዊ

ከሰሐራ በታች ባሉ አገራት ከኤች አይቪ/ኤድስ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር 37 ሚሊዮን እንደሆነ የ2017 ዓለም አቀፍ ዘገባ ይናገራል። ከነዚህ ውስጥ ደግሞ አብዛኞቹ ለዓቅመ አዳም የደረሱ «አዋቂ» ሊባሉ የሚችሉ ወጣቶች ናቸው። ወጣቶች ትኩስ ጉልበት፣ ንፁህ ህሊናና የማይበርድ የለውጥ ስሜት ያላቸው የኅብረተሰቡን ዕድገት የሀገሪቱን አንድነት ለመጠበቅ ተቀዳሚና ተጠቃሚ ኃይሎች መሆናቸውን መጪው ጊዜም የወጣቶች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶ/ር አብይ አህመድ ደጋግመው አስምረውበት ገልፀውታል። ከእሳቸው በላይ ስለወጣቱ ትውልድ መናገር ማዕድ ማበላሸት ስለሆነ አንሞክረውም። አነሳሳችን ከኤች አይቪ/ኤድስ ጋር የተገናኙ ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ነው።
ወጣቶች እጅግ አስደሳችና አካላዊም ሆነ ሁለንታናዊ ውጤት ጐልቶ በሚታይበት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ዕንቁዎች ናቸው። ይህ ዕድሜያቸው የተለያዩ ተግባራትን እንዲሞክሩ ዕድል የሚሰጣቸው በመሆኑ ብዙዎቹ ጠቃሚ ዕድሎች ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ ጐጂ ተግዳሮቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ወጣቶች ሳያስቧቸው ከሚሞክሩዋቸው ጐጂ ሊሆኑ ከሚችሉ ድርጊቶች መካከል ወሲብና ከወሲብ ጋር ተያያዥነት ያላቸው አጋጣሚዎች ተጠቃሾች ናቸው። እነዚህ ድርጊቶች አጋጣሚዎች በአግባቡ ካልተያዙ ለኤች አይቪ፣ ላልተፈለገ እርግዝናና ለሌሎች የአባላዘር በሽታዎች ሊያጋልጡ ይችላሉ። የወጣቶች ለኤች አይቪ ተጋላጭነት የሚመጣው በዋናነት ለኤች አይቪ ካላቸው ግንዛቤ በቂ አለመሆንና ስለወረርሽኙም ያላቸው ግንዛቤ የተዛባ በመሆኑ ነው። ለምሳሌ «ኤች አይቪ የለም» ብለው የሚያስቡ ወጣቶች ልኖሩ ይችላሉ። «ወጣት ስለሆንኩ ኤች አይቪ እኔን አይዘኝም» የሚሉም አይጠፉም «ኤች አይቪ ከጉንፋን አይበልጥም---» ከሚል የተዛቡ አመለካከቶች በመነሳት ጥንቃቄ የጐደለው ወሲብ ከተፈፀመ በኋላ ከኤች አይቪ ይልቅ ያልታቀደ እርግዝናን በመፍራት የድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ እንክብሎችን መወሰድ በአሁኑ ጊዜ በብዙ ወጣቶች ዘንድ ልማድ እየሆኑ መጥቷል።
ከእነዚህ በተጨማሪ ሌሎች ተጋላጭነትን የሚያባብሱ አመሎች ማለትም የአንዳንድ ሱስ አስያዥ ዕጾችን ተጠቃሚነት፣ የወሲብ ፊልሞችን ማየትና በሞባይልና ፌስቡክ በመሣሰሉ ማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ ወሲብ ቀስቃሽ ምስሎችን እና መልእክቶችን መለዋወጥ፣ አሉታዊ ለሆኑ የአቻ ግፊቶች መሸነፍ እና የመሳሰሉት በለጋ ዕድሜያቸው ጥንቃቄ የጐደለውም ግብረ ስጋ ግንኙነት እንዲፈፀሙ የሚገፋፉ ናቸው። በወጣትነት ዕድሜ ያሉ ልጆች ከእንደነዚህ ዓይነት ኃላፊነት ከጐደለውና ለጤና ቀውስ ከሚያጋልጡ ድርጊቶች መቆጠብ ካልቻልን ለኤችአይቪ ኤድስ፣ ለአባላዘር በሽታዎችና ላልተፈለገ እርግዝና የመጋለጥ ዕድላችን ከፍተኛ ይሆናል። በዚህም የተነሳ ወጣቶች ለከፍተኛ የጤና ችግር ከሚዳርጉና የወደፊት ህይወታቸው ከሚያበላሹ ተግባራትና አጋላጭ ባህርያት ራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው።
ወጣቶች ስለኤች አይቪ ምንነት መተላለፊያና መከላከያ መንገዶች ሙሉ ግንዛቤ ለማግኘት ጥረት ማድረግ አለባቸው። ሳያቅዱና ሳይፈልጉ ወደ ግብረ ሥጋ ግንኙነት ከሚገፋፉ ባህርያት ራሳቸውን ማራቅ አለባቸው። ያለንበት ወቅት በርካታ የሆኑ ሌሎች ቀዳሚ ተግባራትና ዓላማዎች ያሉበት በመሆኑ በዚህ ዕድሜ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ማድረግ ደግሞ እነዚህን ተግባራትና ዓላማዎች በስኬት እንዲያጠናቅቁ መሰናክል ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ለምሳሌ ባልተፈለገና ላልታቀደ እርግዝና፣ ለኤችአይቪ እና የአባላዘር ኢንፌክሽኖች የመሳሰሉ አደጋዎችን ሊፈጥር ስለሚችል ከግብረስጋ ግንኙነት መታቀብ ይገባቸዋል። ራስን ከወሲብ ማራቅ ካልተቻለና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ከተገባ ግን ኮንዶምን በትክክልና ሁልጊዜ መጠቀም ተገቢ መሆኑን ማመንና መተግበር አለባቸው።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ትልቅ ግንዛቤ ማግኘት ያለበት አብይ ጉዳይ በመውለድ ዕድሜ ክልል ውስጥ የምትገኝ ሴት ኤችአይቪ በደሟ እንደሚገኝ በምርመራ ከተረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ ልጅ መውለድ ጥንቃቄ የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑ ነው። ይህም በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው የመጀመሪያው ምክንያት ኤችአይቪ በደሟ የሚገኝባት ሴት ከኤችአይቪ ነፃ የሆነ ልጅ ለማግኘት ጥብቅ የሆነ የጤና ባለሙያ ክትትል ምክርና የሕክምና አገልግሎት ማግኘት ያለባት መሆኑ ነው ይህንን ካላደረገች ኤችአይቪ በደሙ ያለበት ህፃን የመውለድ መጥፎ አጋጣሚ ሊያገኛት ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ እርግዝናና ወሊድ በራሳቸው ብዙ የአካል ለውጦችን የሚያስከትሉ ሂደቶች በመሆናቸው አንዲት ኤች አይቪ በደሟ የሚገኝባት ሴት እርግዝናና ወሊድን ስታቅድ በተሟላ የጤንነት ሁኔታ አርግዛ መውለድ እንድትችል የጤና ባለሙያን ምክር ማግኘት አለባት።
ይህንን ካላደረገች ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር ለተያያዙና ለሌሎች የጤና ችግሮች በቀላሉ ልትጋለጥ ትችላለች በዚህም የተነሣ አንዲት ኤች አይቪ በደሟ የሚገኝባት ሴት በታቀደ መልኩ እና በጤና ባለሙያ ምክር ብቻ ልጅ መውለድ ይገባታል። ይህንንም ለማሳካት የሚከተሉትን ምክሮች በተግባር ብታውል ይጠቅማታል። የመጀመሪያ ነገር ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ አስፈላጊ ምርመራዎችን ማድረግ አለባት። ከዚያም ከጤና ባለሙያ በምታገኘው ምክርና ውሣኔ መሰረትና ራሷም በምታደርጋቸው ሁለንተናዊ ዝግጅቶች መሠረት የፀረ ኤች አይቪ መድኃኒት መውሰድ መጀመር አለባት። መድኃኒቱን መውሰድ ከጀመረች በኋላም ያለማቋረጥና በጤና ባለሙያው ትዕዛዝ መሠረት መውሰድ አለባት፡፡ ለጤናዋ ተስማሚ የሆነ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት በመምረጥ ተጠቃሚ መሆን ይገባታል። የግብረ ስጋ ግንኙነት በምታደርግበት ጊዜ ሁሉ በመውሰድ ላይ ካለችው የእርግዝና መከላከያ በተጨማሪ ኮንዶምን ሁሌና በትክክል መጠቀም ይኖርባታል። ነገርግን ለማርገዝ ስትወስንና ውሳኔዋም በሀኪም ተቀባይነት ሲያገኝ ያለኮንዶም ማድረግ ትችላለች፡፡ ልጅ ለመውለድ ውሳኔ ላይ ስትደርስ የጤና ባለሙያዎችን ምክር ማግኘት ብሎም ውሳኔዋን ከጤና ባለሙያዎች ምክር ጋር በተጣጣመ መልኩ ማገናዘብ አለባት እነዚህን የጤና ምክሮችና አገልግሎቶች ከግምት አለማስገባትና አለመጠቀም ውጤቱ ቫይረሱ በደሙ የሚገኝበት ልጅ መውለድ ብሎም በራሷ ላይ ከፍተኛ የሆን የጤና እክል ሊያስከትል እንደሚችል ማወቅ እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው። እነዚህን ጥንቃቄዎች የምታደርግ ኤችአይቪ በደሟ የሚገኝ ሴት የራሷን ጤና በተገቢው መጠን መጠበቅ ትችላለች የምትወልደው ልጅም ከኤች አይቪ ነፃ እንዲሆን የትዳር አጋሯን ጨምሮ ማኅበረሰቡም በዚህ ረገድ ድጋፍ ሊሰጣት ይገባል።
ኤች አይቪ በመርፌ፣ በምላጭ፣ በጥርስ ብሩሽ አማካኝነት የሚተላለፍ ቢሆንም በተለይ በሀገራችን ዋንኛ መተላለፊያው የግብረሥጋ ግንኙነት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋንኛ ተጋላጮች ሴተኛ አዳሪዎች ናቸው። በሀገራችን ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሴቶች በሴተኛ አዳሪነት ተሰማርተው ይገኛሉ። ሴቶችን ወደዚህ ተግባር እንዲገቡ የሚገፋፉ ሁኔታዎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የሆኑ የህይወት አጋጣሚዎች ሲሆኑ ሴተኛ አዳሪነት ከበርካታ የወሲብ ደምበኞች ጋር የተያያዘ መሆኑ ከመጠን ያለፈ መጠጥ መጠቀም ለሱስ የሚያጋልጡ ባህርያት መኖር ኮንዶምን ሁልጊዜና በትክክል ያለመጠቀም እንዲሁም የኤች አይቪ/ኤድስ ወቅታዊ መረጃዎችን ያለማግኘት ችግሮች ለቫይረሱ ከሚያጋልጡ ሁኔታዎች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። በዚህ ምክንያት የኤችአይቪ ስርጭት መጠን በሴተኛ አዳሪዎች ዘንድ ከፍ ያለ ነው።
የኤችአይቪ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ በርካታ ሁኔታዎች አሉ። ኮንዶምን ሁልጊዜ በትክክል መጠቀም፣ ከወሲብ ደንበኞች ጋር በኮንዶም አጠቃቀም ዙሪያ የመደራደር ክህሎት ማሳደግ፣ አሉታዊ የአቻ ግፊትን መቋቋም፣ የኤች አይቪ/ኤድስ ወቅታዊ መረጃዎችን ማግኘት፣ የፀረ ኤችአይቪ ህክምና የአባላዘር በሽታ አና የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎቶች የሚሰጡበትን ቦታ ማወቅና ተጠቃሚ መሆን፣ የተቃና የወደፊት ህይወት ለመምራት የገንዘብ ቁጠባ ባህልን ማዳበር በተለይ ኤች አይቪ ተመርምሮ ራስን ማወቅ ለበለጠ ኃላፊነት እና ለጤናማ አኗኗር መሰረት መሆኑን ማወቅና ማመን ዋንኞቹ የመከላከያ ዘዴዎች ናቸው። በሴተኛ አዳሪዎች ላይ በነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ ብዙ መሥራት ያስፈልጋል።
ተመርምረው ኤች አይቪ በደማቸው ውስጥ የተገኘባቸው ሴተኛ አዳሪዎች የፀረ ኤችአይቪ ህክምና መጀመር የህክምና ክትትል በማድረግ ጤናማ ህይወት ለመምራት እና ቫይረሱ ወደሌላ ሰው እንዳይተላለፍ ማድረግ ይችላሉ። ልጅ ወይም የፍቅር ጓደኛቸው ወይም የወሲብ ደምበኛቸው እንዲሁም ቤተሰባቸው እንዲመረመሩ ግፊት ማድረግ አለባቸው። ቫይረሱ ከእናት ወደ ጽንስ/ልጅ እንዳይተላለፍ የፀረ ኤችአይቪ ህክምና ክትትል ለማድረግ ይረዳል። ድጋፍና እንክብካቤ ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታዎች ለማመቻቸትም ይረዳቸዋል። በአንፃሩ ተመርምረው ኤችአይቪ በደማቸው የሌለባቸው ሴተኛ አዳሪዎች የበለጠ ጥንቃቄና ኃላፊነት የተሞላበት የግብረስጋ ግንኙነት ማድረግ አለባቸው። ባለመመርመር የሚመጣ ጥርጣሬ እና ጭንቀት ለማስወገድ ይረዳቸዋል። ለኤችአይቪ የሚያጋልጡ የግለ ባህርያትን ለይቶ በማወቅ ዘለቄታ ያለው የጠባይ ለውጥ ለማምጣት ይጠቅማቸዋል። ተመርምሪያለሁ! ራሴን ማወቄ የተሻለ ነገን እንዳስብ ረድቶኛል! እናንተም ተመርመሩ! ለማለት ግምባር ቀደም መሆን አለባቸው።
ከላይ ካስቀመጥናቸው የኤች አይቪ ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች ማለትም ከወጣት ወንዶች በመውለድ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሴቶች እና ሴተኛ አዳሪዎች መካከል በሁሉም ክልሎች ወጣት ሴቶች ከወንዶች ይልቅ በይበልጥ ለቫይረሱ ተጋላጭ ናቸው። ከሴተኛ አዳሪዎችም ውስጥ በሀገር ደረጃ 25 በመቶዎቹ በደማቸው ቫይረሱ ይገኛል፡፡ የወሲብ ደምበኞቻቸውም በዚያው መጠን ተጋላጮች ናቸው።

በግርማ ለማ

Published in አጀንዳ
Sunday, 13 May 2018 17:28

ክብር ለእናቶች!

«እናት ለምን ትሙት ትሒድ አጎንብሳ ታበላ የለም ወይ በጨለማ ዳብሳ» የሚል ዘፈን ሲሰማ ሁሉም ሰው እናቱን ያስታውሳል። በዚያው ቅጽበት እናትህ ምንህ ናት ቢባል ብዙ ነገር ይደረድርና በቃ ቃላት የለኝም ብሎ ይዘጋዋል። ምክንያቱም ስለእናት ብዙ ነገር ማለት ስለሚቻል። በተለይ ከሚያዝያ መጨረሻ ጀምሮ እስከዛሬዋ ዕለት የእናቶች ቀን ታስቦ በሚውልበት ዕለት ስለእናቶች ክብር ብዙ የምንሰማው ነገር አለ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶክተር አብይ አህመድ መጋቢት 24 ቀን 2010ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአደረጉት ንግግር «የሰባት ዓመት ልጅ እያለሁ እንዲህ ከፊታችሁ እንደምቆም የምታውቅ እና ይህንን ሩቅ ጥልቅ እና ረቂቅ ራዕይ በውስጤ የተከለች፣ ያሳደገች እና ለፍሬ ያበቃች አንዲት ኢትዮጵያዊት እናት እንዳመሰግን በትህትና እጠይቃለሁ። ይህች ሴት እምዬ ናት፤ እናቴ ከሌሎቹ ቅን የዋህ እና ጎበዝ ኢትዮጵያውያን እንደ አንዶቹ የምትቆጠር ናትና ቁሳዊ ሀብት ብቻ ሳይሆን አለማዊ እውቀትም የላትም፡፡
በእናቶች ውስጥ ሁሉንም የኢትዮጵያ እናቶች ዋጋ እና ምሥጋና እንደመስጠት በመቁጠር ዛሬ በህይወት ካጠገቤ ባትኖርም ውዷ እናቴ ምሥጋናዬ ከአፀደ ነፍስ ይደርሳት ዘንድ በብዙ ክብር ላመሰግናት እወዳለሁ፡፡ ሌሎች ኢትዮጵያውያን እናቶቼ በልጆቻቸው የነገ ራዕይ ላይ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው በመገንዘብ ነገ ለሚያፈሩት መልካም ፍሬ ዛሬ ላይ የሚዘሩት ዘር ዋና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ለሚከፍሉት መስዋእትነት ያለኝን በምንም የማይተካ አድናቆት፣ ምስጋና እና ክብር እገልጻለሁ...» ብለዋል፡፡ ይህ ንግግር ብዙዎች እናታቸውን እንዲያስታውሱና የደስታን እንባን እንዲያነቡ አድርጓቸዋል፤በንግግራቸው ኢትዮጵያዊ እናቶች ለልጆቻቸው ያላቸው ዋጋ ምን ያህል ላቅ ያለ ስለመሆኑም ትምህርት የሰጠ ነው።
የእናት ፍቅር የሰው ህሊና ሊመረምረው፤ የሰው ልብ ሊሸከመው አይችልም። ስለዚህ ሆደ ሰፊና ለአገር ሟች፤ ሰዎችን ወዳጅ መሆንን ከእናቶች መማር ያስፈልጋል። ሁሉም ሰው በእናቱ ይመካል፣ ሁሉም ሰው የራሱን እናት የተለየች እንደሆነች ይመሰክራል፡፡ሁሉም የእናቱ ፍቅር፣ መስዋእትነት፤ መከራ፤ ከየትኛውም እናት የበለጠ እንደሆነ ይናገራል። ይህ የመጣው ደግሞ የእናትን ያህል አፍቃሪ ለመሆን እናት መሆን ግድ ስለሚል ነው።
እናትነትን ለመግለፅ ቅኔ ቢደረድሩ፣ ቋንቋ ላይ ቢራቀቁ፣ ዜማ ላይ ቢፈላሰፉ. . . ተገልፆ አያልቅም። እናትነት ጥልቅ ነው፤ ውስብስብ ነው፤ ምስጢር ነው። እናት ልጇ አድጎ ትልቅ ሰውም ቢሆን ራሱን ቻለ አትልም። ለእሷ አሁንም ልጅ ነው። እንደ ልጅነቱ ሁሉ በጉልምስናው ጊዜም ትጨነቅለታለች። በመሆኑም ከራስ ያለፈ ተቆርቋሪነትን፤ እንዲወድቅ አለማሰብን ከእናትነት የምንወስደው ልዩ ባህሪ ሊሆን ይገባል።
ፈጣሪ ነች የምትባለው እናት ኢትዮጵያ ውስጥ ለየት ያለ ትርጓሜ ይሰጣታል። ለምሳሌ አብዛኛዎቹ አውሮፓውያን እናቶች ልጆቻቸውን እስከ 18 ዓመት ድረስ ካሳደጉ በኋላ ለመተያየት እንኳን አይፈልጉም። ልጆችም ራሳቸውን ከቻሉ ወደ ወላጆቻቸው እምብዛም አይመጡም። ለአብነት ያህል ኖርዌያውያን፣ ጀርመናውያን እና የሌሎችም እናቶች በልጆቻቸው ናፍቆት እንደሚሰቃዩ ጥናቶች ያሳያሉ። እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን እናትና ልጅን የሚለያያቸው ሞት ብቻ ነው። ፍቅራቸው እስከ መቃብር ይወርዳል።
ይህንን ለማጠናከርም አበው “እናትነት እውነት፣ አባትነት እምነት ነው” ይላሉ፡፡ ምክንያቱም እናት ከእርግዝናዋ ጀምሮ እስከ ምጧ ድረስ በጭንቀት ታሳልፋለች። ከዚያም አልፋው በተለይ ኢትዮጵያውያን እናቶች አባትም እናትም ጭምር ሆነው ስለሚያሳድጉ ስቃያቸው የበረታ ነው። ስለሆነም እናቶች ተጎሳቅለው ልጆቻቸው እንዲያምርባቸው፤ ደክመው ልጆቻቸው እንዲበረቱ፤ ከስተው ልጆቻቸው እንዲፋፉ ሳይታክቱ የሚሰሩ ባለውለታዎቻችን ናቸውና ክብር ለእናቶች ይገባል።
የእናት ጥበብ የመኖርን ጥበብ ለልጆች ያስተምራል፤ የእናት ልብ የሕፃናት ትምህርት ቤት ይሆናል፤ እናት ጉዳታችንን እና ጭንቀታችንን ሁሉ የምንቀብርበት ስፍራ ናት። እናት ምግብ ናት፣ ፍቅር ናት፣ ምድር ናት፡፡ በእርሷ መወደድ ማለት በሕይወት መኖር፣ ስር መስደድና መታነጽ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን እናቶች ደግሞ ይህንን ሁሉ ያሟላሉ።
ለእናቶች ክብር መስጠት ሲባል ለእናቶች ቀን ስጦታ ከመስጠት በላይ ዘወትር አክብሮት ማሳየት ነው። ሁሉም ሰው ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌላውም እናት ክብር ሊሰጥ ይገባል፡፡ እናቶችን ማክበርና ፍቅር ማሳየት ትልልቅ ስጦታ በመስጠት ብቻ ሳይሆን ለመስዋዕትነታቸው እውቅና በመስጠትም ነው።
እናት ስቃይዋ ከንቱ እንዳልቀረ በማሳወቅ፣ ሰው እንደወለደች እንድታውቅ መልካም ሰው ሆኖ በማሳየት፣ ህመሟ ልፋትዋ ውሃ እንዳልበላው በሥራ በመተርጎም፣ ደግነቷን ሳይበርዝ ለቀጣዩ ትውልድ በማስተላለፍና የምትፈልገውን ሙሉ አድርጎ በማሳየት ክብሯን መግለጽ ያስፈልጋል። እናት ሌሎች እናቶች እንደ እርሷ ሆነው ማየት ትፈልጋለች። ብዙዎች ለእናታቸው ማድረግ የማይፈልጉትን በሌሎች ላይ ሲተገብሩት ስታይ ያማታል፤ አልፎ ተርፎ እናቶች ይከበራሉ በሚባልበት የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ውስጥ በአደባባይ እናቶችን የሚያዋርዱ ስድቦች እንዲህ የተለመዱ ሲሆኑም ቅስሟ ይሰበራል። እናም ለእናት ክብር ሲሰጥ ይህም ግምት ውስጥ መግባት አለበት። ዘላለማዊ ክብር ለእናቶች ይሁን!

Published in ርዕሰ አንቀፅ
Sunday, 13 May 2018 17:27

ጥቂት ስለኦቲዝም

አለማችን በሚያስደንቁ ተፈጥሯዊ ነገሮች የተሞላች ነች። ልጆች በሳይንሳዊ ምርምር እና የሰው ልጅ በግሉ ሁሉንም የተፈጥሮ ሚስጥሮች መረዳት አለመቻሉ ምን ያህል ረቂቅ (ጥልቀት ያለው) እንደሆነ የሚያስረዳን ነው። እኛ የሰው ልጆች ደግሞ ከሁሉም ፍጥረታት ለየት የሚያደርገን አለማችን ላይ ያሉ ልዩ ነገሮችን ለመረዳት በምናደርገው ጥረት እና ጉጉት ነው። ታዲያ የሰው ልጆች ፍላጎትን ተመስርተን አመቺ በሆነ አጋጣሚ ሁላ ለእናንተ በዚህ ገፅ ላይ ስለ የምናጋራችሁ ጉዳይ አለና ዛሬ ቀኑን የዋጀ ነገር እንነግራችኋለን። ስለ ኦቲዝም ምንነትና መደረግ ያለበት ጉዳይ ነው የምናወጋችሁ። ምክንያቱም ልጆች በፈረንጆቹ አፕሪል የኦቲዝም ቀን ሆኖ ይከበራል። በሽታው ደግሞ እኛም አገር ያለ በመሆኑ እንዳገርም ይህንን ወር ከዚህ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ጉዳዮች ይዳሰሳሉ። ስለሆነም እኛም በዚህ ዙሪያ ጥቂት ልንላችሁ ወደድን። መልካም ንባብ ይሁንላችሁ።
ኦቲዝም የቃሉ መሰረት Autos ከሚለው የግሪክ ቃል የተገኘ ሲሆን፤ ትርጉሙም ራስ ማለት ነው። ይህ ችግር ያለባቸው ልጆች ራሳቸውን ከሌላው ማህበረሰብ በማግለል የራሳቸውን አለም እንደሚፈጥሩ ለማመልከት የተወሰደ ቃል ነው። ኦቲዝም ቋሚ የሆነ የማህበራዊ ተግባቦትና ግንኙነት ችግር ሲሆን፤ አዕምሮ በሚፈለገው ደረጃ በሚያስፈልጉ ክህሎቶች ማደግ እና መበልፀግ ሳይችል ሲቀር ይህ ይፈጠራል። ኦቲዝም በአብዛኛው ከ2 ዓመት እድሜ ላይ ካሉ ልጆች የሚጀምር ወይም የሚታይ ሲሆን፤ ከሴቶች ይልቅ ወንዶች ላይ በብዛት ይስተዋላል።
የኦቲዝም ምልክትን በተመለከተ በዋናነት የሚጠቀሱት ማህበራዊ ግንኙነት አለማድረግ፣ ዓይን ለዓይን መተያየትን መፍራት፣ በአንጻሩ ደግሞ የተናጋሪውን አፍ ላይ ማተኮር፣ ቋንቋን ለማዳበር ረዘም ያለ ጊዜ መፍጀት ናቸው። በተመሳሳይ የሚሰሙትን ቃላት እና አረፍተ ነገሮች መደጋገም፣ ከተመሳሳይ የዕድሜ አጋሮቻቸው ጋር ግንኙነት የመመስረት ችግር መኖር፣ ውስን የሆኑ የሰውነት እንቅስቃሴዎች ማድረግ፣ ሌሎች ልጆችን የሚያጓጓ እና የሚያስደስት ነገር እነሱን አለማስደሰቱም ምልክቱ ነው።
ተደጋጋሚ የሆኑ ባህርያትን ማሳየት፣ በዚህ ጊዜ ራሳቸውን ሊጎዱ መቻላቸውም ሌላው መለያው ነው። ስለዚህም ነገሮች ከተለምዷዊው ሁኔታ ወጣ ሲሉ አይወዱም፣ ለተወሰኑ ድምጾች እና ሽታዎች እጅግ በጣም ስሜታዊ እና ያልተለመደ ምላሽ ሊኖራቸው ይችላል። ለመሆኑ እንዲህ አይነት ባህሪ የሚያሳዩ ልጆችን እንዴት ማገዝ እንደምትችሉ ታውቃላችሁ? መጀመሪያ ማወቅ ያለባችሁ ኦቲዝም በህክምና ብቻ ሳይሆን እናንተን በመሰሉ ልጆች መታገዝ ሲቻል ነውና ብዙ ማድረግ ያለባችሁ ነገር አለ። ለምሳሌ ከእነርሱ ጋር መቀራረብ የልጆቹን ሁለንተናዊና አዕምሮኣዊ እንዲሁም አካላዊ እድገታቸው እንዲፋጠን ይረዳቸዋል። እናንተም ይህንን ማድረግ አለባችሁ።
የሚፈልጉትን ነገር አብራችኋቸው ማድረግና በማሳመን ችግር እንዳይደርስባቸው መንከባከብ ይጠበቅባችኋል። አካባቢያችሁን ለልጆቹ ምቹ ማድረግ እና ከመምህራኖቻቸው ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዲፈጠርላቸው በማግባባትና መምህሮቻቸው እንዲያግዟቸው በማድረግ መርዳት ትችላላችሁ። የየዕለት ልዩነታቸውን እና እድገታቸውን በመከታ ተልም ለውጥ እንዳላቸውና ሁልጊዜ የሚያስደ ስት ነገር እየሰሩ እንደሆነ ልትነግሯቸውና ልታበረታቷቸውም ያስፈልጋል።
እነርሱ የማይችሉት ነገር ግን እናንተ ችሎታው ያላችሁን እውቀት በማጋራትም የቋንቋ ብቃቱን ልታዳብሩለት ትችላላችሁ። አብራችኋቸው ረጅም ጊዜ ማሳለፍና ከእናንተ ጋር እንዲጫወቱ ማድረግ ከቻላችሁም ትልቅ እገዛን አድርጋችሁላቸዋል። በኦቲዝም የተያዙ ልጆች ተራ መጠበቅም ሆነ መተባበር አያውቁበትም፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን ብቻቸውን መጫወትን ይመርጣሉ፡፡ ጫወታዎቻቸውም ቢሆን ከተለመዱት ወጣ ያሉ ናቸው፡፡ በዚህ ወቅት ደግሞ እናንተን ሊረብሿችሁ ይችላሉ። ስለዚህ ይህንን ሲያደርጉ ስታዩ እናንተ መጣላት የለባችሁም። ይልቁንም ልትረዷቸው ይገባል። ያልተቋረጠ ፍቅርን በመስጠት፣ ወጥ ባህሪን በማሳየት፣ እንክብካቤን ባለማጓደልም እርዷቸው እሺ? በሉ ለዛሬ ይህንን እንድታደርጉ በማሳሰብ ልሰናበታችሁ። መልካም እለተ ሰንበት።

ጽጌረዳ ጫንያለው

Published in ማህበራዊ

ልጆች እንዴት ናችሁ? የሳምንቱ ትምህርት እንዴት አለፈ? እርግጠኛ ነኝ ቆንጆ ነበር። ጠንካራ ተማሪ መሆን ቤተሰብን ብቻ ሳይሆን አገርን ያኮራል። እራስንም ቢሆን ያስከብራል አይደል? በተለይ ደግሞ በተሰጥኦ ላይ ተመስርታቸሁ የምትሰሩ ከሆነ ዋጋው ከፍ ያለ ነው። ልጆች ተሰጦ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ታውቃላችሁ? ተሰጦ የአንድ ሰው ልዩ ብቃት ነው። ለምሳሌ እኔ የሂሳብ ትምህርትን ከሌሎቹ በተለየ መልኩ የምወድ እና የምችል ከሆነ «የሂሳብ ትምህርት ተሰጦ አላት» ይባላል።
ለመሆኑ ልጆች ምን መሆን እና በህይወታ ችሁ ምን ማድረግ እንደምትፈልጉ ለይታችሁ ታውቃላችሁ? ተሰጦዬ ይህ ነው በማለትስ ወደተግባር የገባችሁበት አጋጣሚ አለ? አናውቅም የሚል መልስ የምትሰጡ ካላችሁ ስጦታን ቀድሞ ማወቅ ለቀጣይ ስራችሁ እንደሚጠቅማችሁ መገንዘብ ይኖርባችኋል፡፡ ካላወቃችሁ ግን ምርጫችሁ ስለሚሰፋ ማድረግ የምትፈልጉትና በቀላሉ መለየት እንዳትችሉ ያደርጋችኋል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ውጤታማነታ ችሁ ይቀንሳል፡፡ ስለዚህ ተሰጧችሁን ቀድማ ችሁ ማወቅና በዚያ ላይ ያተኮረ ተግባር ማከናወን ይኖርባችኋል፡፡
አንዳንዶቻችሁ ያላችሁን ተሰጦ ከወዲሁ አውቃችሁ ይሆናል። ይህ ደግሞ የተነቃቃችሁ እና በቀላሉ ውጤታማ እንድትሆኑ ያደርጋች ኋል፡፡ ነገር ግን በተጨማሪ አንድ ጉዳይ መገንዘብ ይኖርባችኋል። ፍላጎታችሁ ጋዜጠኛ፣ ሰዓሊ፣ መምህር፣ ዶክተር፣ ፓይለትና የመሳ ሰሉትን እያላችሁ የሙያ ዘርፎችን ዘርዝራችሁ ይሆናል። ነገር ግን ይህንን የመረጣችሁትን በተግባር ካላስደገፋችሁት በምንም መልኩ ልዩ ችሎታችሁን ልታውቁ አትችሉም፡፡ ልክ አናውቅም እንዳሉት ልጆች ምኞታችሁን ልታሳኩ አትችሉም፡፡ ስለሆነም ከእነርሱ የምትለዩት ልዩ ችሎታችሁን በማወቅ ነውና ለውጤታማነታችሁ ልዩ ተሰጧችሁን በሥራ ማጎልበት ይኖርባችኋል፡፡
ይሁንና ይህንን ችሎታችሁን እንዳታወጡትና ጥቅም ላይ እንዳታውሉት የሚገድባችሁ ነገር ሊኖር እንደሚችል ግምት ውስጥ ያስገባ ስራ መከወን አለባችሁ፡፡ ለምሳሌ የቤተሰቦቻችሁ እገዛ አናሳ መሆን፣ የመምህሮ ቻችሁ ድጋፍ በምትፈልጉት መልኩ አለመሆንና መሰል ጉዳዮች ፈተና ሊሆንባችሁ ይችላሉ፡፡ ሆኖም እናንተ ግን እችላለሁ፣ ምኞቴን አሳካለሁ እንጂ አልችልም፣ አላደርገውም ማለት የለባችሁም፡፡ ይልቁንም እነርሱን ለማሳመን የምትችሉትን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅባችኋል፡፡ ከዚያ የምታደርጉትን ነገር ሲረዱ ደጋፊያችሁ ይሆናሉ፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድ ታሪክ ላጫው ታችሁ፡፡ አንድ ተማሪ ነበረ፡፡ ልዩ ችሮታው ስዕል መሳል ነው፡፡ ዘወትር በተሰጠው ደብተር ላይ ስዕሎችን በመሳል ያሳልፋል፡፡ ስዕል ለእርሱ ሀሳቡን መግለጫ፣ ጭንቀቱን ማስረሻ፣ ፍላጎቱን ማውጫ ነው፡፡ ስለዚህም በሚረዳውና ሀሳቡን በሚገልጽበት መልኩ ሁሉ እየተማረ እንኳን ይስላል፡፡ በወቅቱ አብዛኞቹ ወላጆች እና መምህራን ስዕል ላይ የሚያተኩር ተማሪ ሰነፍ ነው የሚል እሳቤ ነበር። በመሆኑም ወላጆች ልጆቻቸውን ስእል እንዲስሉ አያበረታቷቸ ውም። ስእል የሚስሉ ተማሪዎችም ሰነፍ ተማሪዎች ናቸው የሚል ድምዳሜ አላቸው፡፡ ልጁም በቤት ውስጥም ሆነ በትምህርት ቤት ስእል መስራት ያበዛ ነበር። ይህን ተግባሩን አንዳንድ አስተማሪዎች አይወዱለትም ነበር።
በአንድ ወቅት አንድ መምህሩ ልጁን እንደሁልጊዜው ሁሉ ስእል ሲሰራ ያገኘዋል። በድርጊቱም በጣም ይናደድና ወላጅ እንዲያመጣ ያዘዋል፡፡ ቤተሰቡም ትምህርት ቤት ይመጡና የተጠሩበትን ምክንያት ከመምህሩ ይረዳሉ፡፡ «ልጃችሁ ትምህርቱን በሚገባ እየተከታተለ አይደለም፣ ሁልጊዜ ደብተሩ ላይ ምንም የማይገባ ስዕል እየሞነጫጨረ በአግባቡ የሚሰጠውን ትምህርት እየተከታተለ አይደለም፡፡ ስለዚህ ልትመክሩት ይገባል» ይላቸዋል፡፡ አባቱም በጣም ተናደው ለካ «ዝም ብዬ ነው ደብተር የምገዛው፤ ደግሞ ስዕል የሚስል ሰነፍ ተማሪ ነው፡፡ ስዕል የሚሳለው በትርፍ ጊዜና ስራ ሲፈታ ነው፡፡ ስለዚህም ሁለተኛ ይህንን የምታደርግ ከሆነ ትመታለህ» በማለት ልጁን ይቆጣዋል። ድርጊቱን እንዳይደግመውም ይመክረዋል። ልጁ ለአባቱ ምን አይነት ምላሽ እንደሰጠ ታውቃላችሁ ልጆች?
አባቴ አትናደድብኝ እኔ ሰነፍ ተማሪ አይደለሁም፤ ይልቁንም ማንም ሳይበልጠኝ ከትምህርት ቤቱ አንደኛ ነው የምወጣው፡፡ ለዚህም ስም ጠሪዬ ጋር ሄደህ ውጤቴን መመልከት ትችላለህ፡፡ በእርግጥ ስዕል እወዳለሁ፤ እስላለሁም፡፡ ይህንን የማደርገው ደግሞ የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ነው፡፡ መምህሮቼ ሲያስተምሩኝ በሚገባኝ ቋንቋ በስዕል ትምህርቱን አስቀምጠዋለሁ፡፡ ስለዚህ ከአዕምሮዬ የተማርኩት እንዳይጠፋ የማደር ግበት ዘዴ ነው እንጂ ሰነፍ ተማሪ ሆኜ አይደለም፡፡ ስለዚህ ከዚህ በኋላም አንተ መረዳት ያለብህ ተሰጥኦን ወደ ተግባር መቀየር ለበለጠ ጉብዝና ያበቃል እንጂ አያሰንፍም፡፡ ስዕል መሳልም እንዲሁ የሰነፎች አይደለም» በማለት ትክክለኛ ምላሹን ለአባቱ ይነግራል፡፡
አባቱ የተናገረው ንግግር ትክክል መሆኑን ቢረዱም ማረጋገጥ ነበረባቸውና ወደ ስም ጠሪው መምህር ጋር በመጓዝ ይጠይቃሉ፡፡ እርሳቸውም ልጁ ውጤታማና ጎበዝ እንደሆነ ያስረዳቸውና ነገር ግን ማስታወሻ የሚይዝበትና የሚማርበት ደብተር መለየት እንደሚጠበቅበት ይነግራቸዋል፡፡ በስዕል ነገሮችን የሚረዳበት መንገድ ለውጤቱ መሰረት ሆኖታል፡፡ ነገር ግን በንጽህና ትክክለኛ የተማሩትን ነገር በተገቢው ደብተር ላይ ማስፈርም ዋጋ እንዳለው ልጁ ማወቅ አለበት በሚልም አስተያየት ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚያ እርሳቸውም ሀሳቡን ተቀብለው እንደማስታወሻ የሚጠቅመ ውን ደብተር በመግዛት የስዕል ችሎታውን እንዲያዳብር አገዙት፡፡ አያችሁ ልጆች ነገሮችን ሳይረዱ መናገር ይጎዳል፣ ይጸጽታልም፡፡ ማሳመን ደግሞ ዋጋው የላቀ ነው፡፡ ስለዚህ እናንተም ማድረግ ያለባችሁ እንደ ጎበዙ ተማሪ ልዩ ተሰጧችሁን ለማጎልበት መበርታት ነው፡፡ የሚያጋጥሟችሁን ፈተናዎችም በብልሃት እንደልጁ ማለፍ አለባችሁ፡፡ በሉ ለዛሬ በዚህ እንሰነባበት በቀሪ ጊዜ ሌላ ጉዳይ ይዤላችሁ እመጣለሁ፡፡ መልካም እለተ ሰንበት ይሁንላችሁ፡፡

ፅጌሬዳ ጫንያለው

Published in ማህበራዊ

 

በአገሪቱ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች የተካሄደ ጥናት በሱስ የተጠቁ ወጣቶች ቁጥር ከፍ እያለ መምጣቱን ያመለክታል፡፡ ቁጥሩ ምን ያሳያል? ምክንያቱስ?
የአሜሪካ ዓለምአቀፍ ልማት (ዩ.ኤስ.አይ.ዲ.) እ.አ.አ. በ2017ይፋ በአደረገው ጥናት፤ በኢትዮጵያ የወጣቶች የሱስ ተጠቂነት ቁጥር መጨመርን ሊያመላክት የሚችል ጥቅል መረጃ ባይኖርም በዩኒቨርሲቲዎች በተደረገ ተከታታይ ጥናት እ.አ.አ. ከ2016 ጀምሮ በከተማም ሆነ በገጠሪቱ ክፍል የሱስ ተጠቂ ወጣቶች ቁጥር ከፍተኛ ነው።
እ.አ.አ. በ2017 ይፋ በተደረገ ጥናት አዲስ አበባና ቡታጅራ አካባቢ ያለው የዕፅ ተጠቃሚዎች ቁጥር አይሏል። ነገር ግን እያንዳንዱን የዕፅ ዓይነት በተናጠል በማድረግ የሚታይበት ሁኔታ አለ። ዩኒቨርሲቲዎች ያጠኗቸው ጥናቶችም ከዚህ ጋር ተያያዥ ናቸው። ለምሳሌ ማሪዋና (ሀሺሽ) በግልጽ መጠቀም ስለማይቻል የተጠቃሚዎችን መጠን በቁጥር መግለፅ ባይቻልም በተደረገው የዳሰሳ ጥናት የተጠቃሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ መምጣቱን መረጃው ያመለክታል።
በሀረሚያ ዩኒቨርሲቲ እ.አ.አ በ2015 በ1040 ሰዎች ላይ በተካሄደ ጥናት 62 ነጥብ 4 በመቶ የሚሆኑት በአደንዛዥ ዕፅነት ከተመደቡት ውስጥ አልኮልን የሚጠቀሙ 50.2 በመቶ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እ.አ.አ. በ2014 መጨረሻ ላይ በተካሄደ ጥናት ደግሞ በጎንደርና አካባቢዋ 48 ነጥብ 23 በመቶ የሚሆኑ ወጣቶች የአልኮል ተጠቃሚ ሲሆኑ፤ ቀሪዎቹ ሲጋራና ጫት ይጠቀማሉ።
አክሱም ዩኒቨርሲቲ እ.አ.አ በ2012 በ764 ሰዎች ባደረገው ጥናት ደግሞ የወጣቶች የሱስ ተጠቃሚነት ቁጥር በጫት 27 ነጥብ 9 በመቶ ሲሆን፣ በአልኮል ደግሞ 32 ነጥብ 8 በመቶ፣ ሲጋራ የሚያጨሱት ደግሞ 9 ነጥብ 3 በመቶ ደርሰዋል።
ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በሰሜን ምዕራብ አካባቢ እ.አ.አ በ2014 በ845 ሰዎች ላይ ባደረገው ጥናቱ ሲጋራ የሚያጨሱት ወጣቶች ቁጥር 11ነጥብ3 በመቶ ሲሆን፤ አልኮል የሚጠቀሙ 35 በመቶና ጫት የሚቅሙ ደግሞ 30ነጥብ 8 በመቶ እንደሆኑ አረጋግጧል። በተመሳሳይ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም 1ነጥብ4 በመቶ አልኮል የሚያዘወትሩ፣ 14 ነጥብ1በመቶ ጫትና 8ነጥብ7 በመቶ ደግሞ ሲጋራ የሚያጨሱ ወጣቶች መኖራቸውን ጥናቱ ያመለክታል።
ጅማ ዩኒቨርሲቲም በአካባቢው እ.አ.አ 2016 በ651ተማሪዎች ላይ ባደረገው ጥናት ጫት፣ ሲጋራና አልኮል በተከታታይነት የሚጠቀሙ ወጣቶች ቁጥር 33 ነጥብ 1 በመቶ፣ 21 ነጥብ 3 በመቶ እና 36 ነጥብ 4 መሆኑን ያትታል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአደንዛዥ ዕጽና ወንጀል ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት እ.አ.አ በ2008 ባደረገው ጥናት እንዳስቀመጠው፤ የወጣቶች የሱስ ተጠቂነት ቁጥር ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ መጥቷል። ለዚህም ምክንያቱ በከተማ ማህበረሰብ ውስጥ አነስተኛ ቁጥር ላላቸው የገጠር ነዋሪዎች የሀሽሽ መድኃኒት እና የመዝናኛ ንጥረ ነገር በስፋት መቅረቡ፣ ዝቅተኛ ዋጋ እንዲኖረው መደረጉ፣ ወጣቶችንም ለተጨማሪ ገቢ ምንጭነት መጠቀማቸው ነው ይላል።
በአብቹ መታሰቢያ ልዩ የአዕምሮ ህክምና ክሊኒክ የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ታደሰ በዳሳ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ የመጨመሩ ምክንያት በአገሪቱ ላይ የቴክኖሎጂ መስፋፋት፣ የሚታዩ ፊልሞችና የሚሰሩ ፊልሞች በግብዓትነት የሚጠቀሟቸው ቁሶች ሱስ አምጪ መሆናቸው፤ በፊልም ላይ የሚሳተፉትም ሆኑ የሚያዩት ወጣቶች መሆናቸው፣ ነጋዴው ማህበረሰብ ሕግ ስላልወጣለት ወጣት ተኮር ሥራ መስራቱ፣ የመንግሥት የሕግ ከለላ አናሳ መሆኑ፤ በተለይም ሕጋዊ ተብለው በሚሸጡት አደንዛዥ ዕፆች ዙሪያ ትኩረት አለመደረጉ፣ ክትትሉም ደካማ መሆኑ፣ ወጣቱ በድብቅ ማድረግን የሚሻ በመሆኑ ድብቅ ቦታዎች መስፋታቸው በዋናነት ይጠቀሳሉ።
ዶክተር ታደሰ መገናኛ ብዙኃን፣ የአደንዛዥ ዕፆች ነፃ ዝውውር፣ የቤተሰብ ሁኔታ፣ የመዝናኛ ቦታዎች በበቂ አለመኖርና ያሉትም በቂ ክትትል ያልተደረገላቸው መሆን፣ የኅብረተሰብ የግንዛቤ ክፍተት የመሳሰሉት ለተጠቂዎች ቁጥር መጨመር መንስኤ እንደሆኑ ይናገራሉ።
ማህበራዊ ኃላፊነት ያለባቸው ተቋማት የተሰጣቸውን ኃላፊነት አለመወጣታቸው ማለትም የሃማኖት ተቋምትና አባቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ወላጆችና የንግድ ተቋማት፣ የአካባቢ ማህበረሰብና የሕግ አካላት ለወጣቱ የሱስ ተጠቂነት ቁጥር ከፍ ማለት ተጠያቂዎች ናቸው ያሉት ዶክተር ታደሰ፤ ወጣቶች በእነዚህ ችግሮች ውስጥ ማለፋቸው የተጽዕኖው ሰለባ ከመሆናቸው በተጨማሪ የመማሪያ ማዕከል (ሞዘቲክ ሴንተር) የሚባለውን የአዕምሯቸው ክፍል ስለሚጎዳ በእውቀት የተመራ ሥራ ለመስራት ይቸገራሉ ብለዋል።
የዶክተር ግንባሩ ሳይካትሪስት ክሊኒክ ባለቤትና የአዕምሮ ስፔሻሊስቱ ዶክተር ግንባሩ ገብረማርያም በበኩላቸው፤ የወጣቶች የሱስ ተጠቂነት ቁጥር መጨመር ምክንያት ራስን ለመደበቅ መሞከር፣ ህመምን ለመርሳት አደንዛዥ ዕፆችን በተከታታይነት መጠቀም፤ ለማጥናትና ሥራን በቀላሉ ለማከናወን ሲባል ከመጠን ያለፈ ዕፅ መውሰድ፤ ለመዝናናትና ከህመም ለመዳን ዕፅን መጠቀም፤ ማህበራዊ ግፊቶችና የአቻ ጓደኛ ግፊቶች ናቸው ይላሉ።
እንደ ዶክተር ግንባሩ ማብራሪያ፤ ሱስ የጭንቅላት በሽታ ሲሆን ለማገናዘብ የሚያስ ችለውን የአዕምሮ ክፍል በቀጥታ ያጠቃል። ማዕከላዊ የአዕምሮ ክፍልም ሥራውን እንዲያቆም ያደርጋል። በመሆኑም ወጣቶች ተምረው እንዳልተማሩ ይሆናሉ። በእርግጥ መጀመሪያ ዕፅን የመጠቀም ሁኔታን የሚጀምሩት በቅድሚያ በቤተሰብ ቁጥጥር ሥር የነበሩ ወጣቶች ለትምህርት ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ ከቤተሰብ ቁጥጥር ውጪ ስለሚሆኑ ያገኙትን ነፃነት በመጠቀም በፈቃደኝነት እንዲሁም በአቻ ግፊትና ሰበብ ነው። ከዚያም በተደጋጋሚ ልምድ ይሆንና ይቀራል። በቀላሉም መውጣት የሚቻልበት ሁኔታ የለም። ስለዚህ ባለበት ላይ የተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ ቁጥሩም በዚያው ልክ ከፍ ማለቱ እንደማይቀር ያስረዳሉ።
የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እ.አ.አ. በ2017 ባወጣው መረጃ፤ በዓለም 700 ሚሊዮን የሚሆኑ ወንዶች ትንባሆን ይጠቀማሉ። በብዛት ደግሞ ታዳጊ አገሮች ውስጥ ይታያል፤ በተለይ በከተሞች አካባቢ ችግሩ የገነነ መሆኑን ያስቀምጥና በአብነት አዲስ አበባን ያነሳል። 31 ነጥብ 4 የሚሆኑት ወጣቶች አደንዛዥ ዕጹን እንደ ሚጠቀሙ ያስነብባል።
በ1995 ዓ.ም በአዲስ አበባ እና በ 24 ከተሞች በአደገኛ ዕፅ እና የተከለከሉ ንጥረ-ምግቦች ዙሪያ በተደረገው ጥናት እንደታየው፤ 69 ነጥብ ሦስት በመቶ የሚሆኑ ወጣቶች ሱሰኛ ናቸው።
የወጣቶች የሱስ ተጠቂነቱ እያሻቀበ በመጣው መጠን እያደገ የሚሄድ ከሆነ፣ መንግሥት በነጋዴዎችና በሕገወጥ መንገድ ዕፆችን በሚያዘዋውሩ ላይ አስተማሪ እርምጃ የማይወስድ ከሆነ፣ ሕጋዊ ባደረጋቸው ሥራዎችም ላይ ሰፊ ክትትል ካላደረገ፣ የሕግ ከለላው ጠንካራ ካልሆነና የፖሊሲ ማዕቀፎቹ እንደሁኔታው ታይቶ ካልተሻሻሉ፣ ማህበራዊ ኃላፊነት ያለባቸው አካላት በጉዳዩ ላይ ከቢዝነስ ባለፈ ሥራ የማይሰሩ ከሆነ፣ ሁሉም መገናኛ ብዙኃን የማስተማሪያ ስልቶችን እየለዋወጡ ግንዛቤ እንዲሰርፅ ካላደረጉና ማስታወቂያዎች ሲተላለፉ ሕጋዊ ርምጃ ካልተወሰደ፤ በሱስ የተያዘ ወጣት ቀጥታ የሚጎዳው አዕምሮው ስለሆነ ጊዜያዊ እውቀት እንጂ የሚቆይ እውቀት አይኖረውም፤ ሥራዎችንም ለማከናወን አቅም ያንሰዋል፤ ይህ ደግሞ በአገሪቱ ላይ እውቀት ያለው ሠራተኛ እንዳይኖር ያደርጋል።
በተጨማሪም በተማረ ኃይል የሚመራ ሥራም አይኖርም። አገሪቱን በኢኮኖሚ የሚደግፍ ወጣት ቁጥር አነስተኛ ይሆናል፡፡ ወጣቶች በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ውስጥ እንዲሳተፉ፣ ያልተፈለ ግብረስጋ ግንኙነት እንዲያደርጉና በበሽታ እንዲጠቁ ይሆናል። የሥራ ብቃትና ምርታማነት ይቀንሳል፣ ማህበረሰባዊ መገለልም ያስከትላል። በተለይ አገር ላይ የሚደርሰው ጫና በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካው እንዲሁም በማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከፍተኛ ይሆናል። 

ዜና ትንታኔ
ጽጌረዳ ጫንያለው

Published in የሀገር ውስጥ

 

ከቤትዎ እስከ ሥራ ቦታዎ ወይም ወደሚፈልጉበት ቦታ ሲጓዙ በተሳፈሩበት ታክሲ ውስጥ ዕድሜው ለሥራ ያልደረሰ ልጅ የመኪናውን በር ለመዝጋት ሲታገል አስተውለው ይሆናል። ወደተለያዩ የወዳደቁ አካባቢዎች ከሄዱ ደግሞ አንድ ፍሬ ልጅ ጉሊትም ይሁን ሱቅ በደረቴ እየነገደ ሊመለከቱ ይችላሉ። በአንዳንድ ቦታዎች ላይም ትምህርት ቤት መግባት የነበረባቸው ህፃናት በጎዳና ሆነው ህይወታቸውን ሲመሩ መመልከት የተለመደ ሆኗል።
ቀደም ሲል የነበሩ የህፃናት መብት ለማስከበር ታስበው የሚውሉ ቀናት ደግሞ ተስማሚና ጥራት ያለው፤ ነጻና ተደራሽ ትምህርት ለሁሉም ህጻናት፤ ሁሉም ህፃናት ልዩ እንክብካቤ እና ፍቅር ይሻሉ፤ «ልጆችን ከጉልበት ብዝበዛ እንታደግ» በሚሉ እና ሌሎችም በርካታ መፈክሮች ታጅበው በየዓመቱ ተከብረዋል። ነገር ግን ከዓለማችን ህፃናት አንድ አራተኛው በዘመናዊ ባርነት ውስጥ እንደሚገኙ ከአራት ዓመት በፊት የዓለም አቀፉ የሠራተኞች ማህበር ያቀረበው ጥናት ያሳያል።
አምስት ሚሊዮን የሚሆኑት ህፃናት ከባርነት ባልተናነሰ ሁኔታ ትምህርት ቤት ሳይሄዱ በጉልበት ሥራ ላይ እንደሚሰማሩም ጥናቱ ያመላክታል። ከኃያሏ አገር አሜሪካ በስተቀር ደግሞ ሁሉም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት የሕፃናት መብት ኮንቬንሽን ተቀብለው ለመተግበር ተስማምተዋል። ነገር ግን ከአሜሪካ ይልቅ የአፍሪካ፣ እስያ እና ደቡባዊ አሜሪካ አገራት በአብዛኛው የሕፃናት መብቶች እንደሚጥሱ የዘርፉ ምሁራን የሚስማሙበት ሃቅ ነው።
የአፍሪካ ህፃናት ፖሊሲ መድረክ ዳይሬክተር ዶክተር አሰፋ በቀለ እንደሚሉት፤ ህፃናት በአሳዳጊዎቻቸው ወይም በሌሎች አካላት ስር በሚቆዩበት ጊዜ ህግን መሰረት ያደረገ እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል። በአካላቸው ወይም በሥነልቦናቸው ላይ ጉዳት የሚያመጣ ድብደባ፣ መጥፎ አያያዝ፣ መንገላታት ካጋጠማቸውም ቀጣዩ ትውልድ እና አገር እየተጎዳች ስለመሆኑ ማሰብ ይገባል። የጥቅም ማግኛ ሆነው መብታቸው ሲገፈፍም ተገቢውን የፍትህ መብቶቻቸው እንዲከበሩ እርምጃዎችን እንዲወሰድ መጣር የማህበረሰቡ ሰብዕናዊ ኃላፊነት እስኪሆን ድረስ መስራት አለበት።
«አብዛኛውን ጊዜ በመላው አፍሪካ የመብት ጥበቃ የሚደረግላቸው ወይም የሚታደጋቸው አካል የሚፈልጉ ህፃናት አስከፊ ተግዳሮት ያጋጥማቸዋል» የሚሉት ዶክተር አሰፋ፣ በአፍሪካ የፍትህ ስርዓቱ ለህጻናት ምቹ እንዲሆን የተደረገው ሥራ መልካም ቢሆንም ገና ብዙ ሥራ እንደሚጠበቅ ይናገራሉ። በተለይ አካል ጉዳተኛ ህፃናት፣ በጎዳና ተዳዳሪዎች እና በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ የሆኑ ህፃናት መብቶቻቸው በአያሌው ከሚገፈፉት መካከል እንደሚመደቡ ስለሚታመን አስፈላጊው የህግ ከለላ በተገቢው ሰዓት እንዲፈፀምላቸው ጥረት ማድረግ ይገባል።
የህፃናት መብት ላይ የሚነሱ የፍትህ ስርዓቶች ከመድልኦ እና ሙሰኝነት ነፃ እንዲሆኑም ክትትሉ በየጊዜው መጠናከር እንደሚገባው ይገልጻሉ። ለዚህም ደግሞ በመንግሥት እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደነገጉ ህግጋትን ሙሉ በሙሉ ሳይሸራረፉ መተግበር እንደሚያስፈልግ ነው የሚያስረዱት።
የህጻናት መብቶች ህግጋት ላይ ጥናት የሚያደርጉት ኬንያዊቷ ዶክተር ንካትሃ ሙሩንጊ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ህፃናት ተኮር የፍርድ ሥርዓቶች በመደበኛ እና በኢመደበኛ አሰራሮች ተግባራዊ ይደረጋሉ። በዚህም ህፃናት ስላሏቸው መብቶች ሚናዎች እና ስለሚኖራቸው ቀጣይ ተስፋቸው የግል ማንነታቸውና ምሥጢር መጠበቅ መረጋገጥ ይኖርበታል።
በተለያዩ ዕድሜ ክልል የሚገኙ ህፃናት ፍትህ እንዲያገኙ ጥረት በሚደረግበት ወቅት ስለአያያዛቸው፣ ስለሚፈልጉት ቀጣይ ህይወታቸው መረጃና ምክር ሊያገኙ ይገባል። በመሆኑም አስፈላጊ ካልሆነ በቀር በህግ ፊትም ቢሆን ሊኖራቸው የሚገባን ነፃነት የመገደቡ እርምጃ በችኮላ መፈጸም አይኖርበትም። በተለይ በኢመደበኛው የፍትህ አፈፃፀም ሂደት ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ ወይም ማህበረሰብ ተኮር ፍትህና ተዛማጅ ሥርዓቶች ለህጻናት አስተዳደር እና ቀጣይ የህይወት እርምጃ ያላቸውን አስተዋጽኦ በመገንዘብ ከመደበኛው የፍትህ ሥርዓትና ህግጋት ጋር የተዛመዱ እንዲሆኑ መስራት እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ።
እንደ ዶክተር ንካትሃ ከሆነ፤ በገጠራማው የማህበረሰብ ክፍል ዘንድ ከቅጣት ይልቅ ለአስተማሪ መፍትሄዎች ቅድሚያ ቦታ የሚሰጡ ባህሎችን እንዲያድጉ መትጋት ይገባል። ምንም እንኳን መደበኛው የህፃናት ፍትህ አተገባበር ስርዓት እያደገ ቢመጣም ኢመደበኛ የህፃነት ፍትህ አተገባበር ህፃናት ላይ ጉልህ ጠባሳ እንዳያሳድር ማገዝ ያስፈልጋል። በተለይ ለፍትህ ማጣት እና አድሎ ተጋላጭ የሆኑ የኦቲዝም፣ አልቢኒዝም አካል ጉዳተኛ ህፃናት በኢመደበኛ ፍትህ ስርዓት ውስጥ ጫና እንዳይደርስባቸው መከላከል የሁሉም ኃላፊነት መሆን ይገባዋል። ነገር ግን ከልክ ያለፈው ወግ እና የባህል ጉዳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው መርሆዎች መሰረት እንዳይጥሉ የሚያደርጉ ከመሆናቸው ባለፈ የህፃናት መብቶች አጀንዳ እንዳይጎለብት እንቅፋት ይሆናሉ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የህፃናት መብት ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ቢኒያም ዳዊት እንደሚሉት ደግሞ፣ ህፃናት ሲጎዱ ተገቢው ፍትህ እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ ችግር ውስጥ ከመግባታቸው በፊት መከላከል ስለሚቻልበት መንገድ መነጋገር አስፈላጊ ይሆናል። በዚህ ረገድ በመጀመሪያ ደረጃ የትምህርት አቅርቦት ላይ ነጻ ትምህርት መሰጠቱ ልጆቹ ወደጎዳና እና ጉልበት ብዝበዛ እንዳይገቡ የሚያደርገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
በኢትዮጵያም ልጆች በለጋ ዕድሜያቸው ለጉልበት ብዝበዛ እንዳይጋለጡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ላይ የምግብ አቅርቦት መጀመሩ እና ነፃ ትምህርት መስጠቱ ሊጠናከር ይገባል። የልጆችን ዕድሜ እና አዕምሮ ዕድገት ያገናዘቡ ሥራዎች እንዲሰሩ በማድረግ ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ህፃናትን ማገዝ እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ። የኢትዮጵያ ሁኔታ በተመለከተ አሁን የተጀመሩትን እና ውጤት እያመጡ ያሉትን የማህበራዊ ጥበቃ ሥራዎች ማፋጠን እንደሚገባ ፕሮፌሰር ቢኒያም ይገልጻሉ።
እንደ ፕሮፌሰር ቢኒያም ገለጻ፤ ህጎች በተለይም የህፃናትን መብትን የሚያስከብሩ ባለሙያዎች በበቂ የሰው ኃይል እንዲሰራ ማስቻል ያስፈልጋል። የልጆች ቁጥር እየጨመረ በሄደ ቁጥር መብቶቻቸውን ለማስከበር የሚመደበው በጀትም መጨመር አለበት። በሌላ በኩል ማህበረሰቡን ስለህፃናት መብት ለማስተማር የሚደረገው ጥረት አናሳ መሆን የለበትም። ምክንያቱም ምንም ህጎች ቢወጡና ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ቢጸድቁ ማህበረሰቡ ስለህፃናት መብት ያለውን ዕውቀት ማሳደግ ካልተቻለ ውጤቱ አመርቂ አይሆንም። በመሆኑም በገጠርም ሆነ በከተማ ያለውን ማህበረሰብ በህፃናት በስነልቦና እና አካላዊ ጉዳት ዙሪያ ማስተማርና ችግሮች እንዳይገጥሙት መከላከል የሚችልበትን ሁኔታ ማሳየት ተገቢ ነው። በየጊዜው አስፈላጊው ትምህርት ሊሰጠው ይገባል።

ዜና ሐተታ
ጌትነት ተስፋማርያም

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።