Items filtered by date: Monday, 14 May 2018

በየአካባቢው ታዳጊና ወጣቶች ጊዜያቸውን የሚያሳልፉባቸውና አካላዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉባቸው ሜዳዎች፤ ከቆይታዎች በኃላ ለህንጻ ግንባታ አሊያም ለሌሎች ልማቶች እንዲውሉ ይታጠራሉ። በዚሁ ምክንያትም ወጣቶች በስፖርት ራሳቸውን እንዳያዳብሩም ብቻ ሳይሆን መዋያ አጥተው ሲቸገሩና ቅሬታዎችም ሲነሱ ይስተዋላል። ቅሬታውን ለመፍታትም በየአካባቢው ያሉ ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ማስተር ፕላኑ በሚፈቅደው መልኩ የይዞታ ማረጋገጫና የባለቤትነት መብት እንዲያገኙ የማድረግ ስራው በወጣቶችና ስፖርት ቢሮዎች እየተከናወነ ይገኛል። በተለይ በዚህ ወቅት ከተሞች በአዲስ መልክ ፈርሰው እየተገነቡና በአዲስ ዲዛይን እየተሰሩ ያሉ በመሆኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችንም በትኩረት መመልከት ይገባል።

የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች አስተዳደርን አስመልክቶ በወጣው አዋጅ ቁጥር 729/2004 ላይም፤ ህብረተሰቡ በሚኖርበት፣ በሚማርበትና በሚሰራበት አካባቢ በስፖርት እንቅስቃሴ ተሳታፊ የሚሆንበትን ሁኔታ ማመቻቸትና ለዚህም ዓላማ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲስፋፉና እንዲጠበቁ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ያሳያል። በአዋጁ መሰረት የማዘውተሪያ ስፍራዎቹ ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ ሶስት ይመደባሉ።
ማዘውተሪያዎቹን ከልሎ ስለመያዝ በሚገልጸው አንቀጽ ስርም፤ ማንኛውም የሚመለከተው የአስተዳደር አካል ለስፖርት ማዘውተሪያነት የሚውሉ ስፍራዎችን በገጠሩ እንደ ህዝቡ አሰፋፈር ወይም በከተማ በማስተር ፕላን መሰረት ከልሎ መያዝ እንዳለበት ይጠቁማል። የማዘውተሪያ ስፍራዎቹ ለህዝብ ጥቅም ሲባል በህግ በተደነገገው መሰረት ካልሆነ በስተቀር ሊወሰዱ አይችሉም። ለህዝብ ጥቅም ተብሎ ሲወሰድም በቅድሚያ ለባለንብረቱ ተመጣጣኝ ካሳ መክፈል እና በተወሰደው ቦታ ምትክ ቦታ መሰጠት አለበት።
ኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር በሃገር አቀፍ ደረጃ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመኑ ከያዛቸው ዕቅዶች መካከል የማዘውተሪያ ስፍራዎች ቀዳሚው ነው። በዚህም ከጥርጊያ ሜዳ እስከ ትልልቅ ስታዲየሞች ድረስ የባለቤትነት መብት እንዲኖራቸውና ድንበራቸው ተከብሮ ቋሚ የውድድር ሜዳ እንዲሆኑ ይሰራል። ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዓመት ዝቅተኛ አፈጻጸም ነበር የተመዘገበው። በሁለተኛው የዕቅድ ዘመን ደግሞ ስራውን አጠናክሮ በማስቀጠል ከ22ሺ100 ወደ 46ሺ806 የይዞታ ማረጋገጫ ያላቸውና ደረጃቸው የተለዩ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ለማሳደግ ነው የታቀደው። የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ከተጀመረ ደግሞ ሶስት ዓመታት ተቆጥረዋል። ታዲያ በእነዚህ ዓመታት ምን ያህል ርቀት መጓዝ ተችሏል ለሚለው ያለፉት ሁለት ዓመታት በማሳያነት ቀርበዋል።
በ2008 ዓ.ም በገጠር የይዞታ ማረጋገጫ ያላቸው የቀበሌ ብዛት በዕቅድ 6ሺ931 ተይዞ 1ሺ205 የሚሆነው መከናወኑን ከሚኒስቴሩ የተገኘ መረጃ ያሳያል። በዚሁ ዓመት ካርታና ፕላን ያላቸው የከተማ የማዘውተሪያ ስፍራዎች ላይ 1ሺ398 ታቅዶ የተከናወነው ግን 303 ነው፤ በአንደኛ ደረጃ የማዘውተሪያ ስፍራዎች ሰባት ለመገንባት ታቅዶ አምስት ተገንብተዋል። በሁለተኛ ደረጃ 38 ታቅዶ የተፈጸመው ሰባት፣ በሶስተኛ ደረጃ 61 ታቅዶ 14 ተከናውኗል። የይዞታ ማረጋገጫ ያላቸው ጥርጊያ ሜዳዎችን 8ሺ658 በዕቅድ ላይ ያለ ቢሆንም፤ አፈጻጸሙ ግን 1ሺ 469 ነው።
በ2009 ዓ.ም ደግሞ በገጠር የይዞታ ማረጋገጫ ያላቸው የቀበሌ ብዛት በዕቅድ የተያዘው11ሺ186 ሲሆን፤ 3ሺ378 ብቻ ተከናውኗል። ካርታና ፕላን ያላቸው የከተማ የማዘውተሪያ ስፍራዎች የታቀደው 1ሺ65፤ የተከናወነው ደግሞ 407 ነው። በአንደኛ ደረጃ የማዘውተሪያ ስፍራዎች ለመገንባት የታቀደው አምስት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ሙሉ በሙሉ ከግብ ለማድረስ ተችሏል። በሁለተኛ ደረጃ የታቀደው 48 ሲሆን የተፈጸመው 16፤ በሶስተኛ ደረጃ 168 ታቅዶ 870 ደግሞ ተከንውኗል። የይዞታ ማረጋገጫ ያላቸው ጥርጊያ ሜዳዎችን 14ሺ820 ለማድረስ ቢታቀድም፤ አፈጻጸሙ ግን 3ሺ 861 መሆኑን ሪፖርቱ ያሳያል።
በተያዘው ዓመትም በገጠር የይዞታ ማረጋገጫ ያላቸው ማዘውተሪያዎችን 15ሺ441፣ ካርታና ፕላን ያላቸው የከተማ የማዘውተሪያ ስፍራዎችን 1ሺ767፣ እንዲሁም የይዞታ ማረጋገጫ ያላቸው የጥርጊያ ሜዳዎችን 22ሺ388 ለማድረስ ታቅዶ ነው እየተሰራ ያለው።
የይዞታ ማረጋገጫ የሚያገኙት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የራሳቸው ካርታ ኖሯቸው በወጣቶችና ስፖርት ቢሮዎች የሚተዳደሩ ይሆናል። ይኸውም ቦታዎቹ ለተለያዩ ጉዳዮች እንዳይተላለፉ የሚታደጋቸው ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ በተደጋጋሚ የሚታየው ለተፈለገበት ዓላማ ሳይውሉ እንደታጠሩ የሚቀመጡ መሆናቸውን ነው። በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎቹ ላይ ነዋሪዎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የማያደርጉበት ከሆነም ለሌሎች አገልግሎቶች መፈለጉ አይቀሬ ነው። በመሆኑም የማዘውተሪያ ስፍራዎቹ ባለቤቶች ቦታውን ከመከለል ባሻገር ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ ምቹ የማድረግና መሰረተ ልማቶችን በማሟላት አገልግሎት እንዲሰጡና ውድድሮችም እንዲካሄዱባቸው ማድረግ መሰረታዊ ጉዳይ ነው።
በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የይዞታ ማረጋገጫ ላይ በተከናወሰው ስራ የተሻለ አፈጻጸም ያሳየው የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መሆኑን የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ያረጋግጣል። የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ የስፖርት ፋሲሊቲ ዳይሬክተር አቶ ባንተአምላክ ሙላት፤ በክልሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ስራዎች እንደ ሌሎች የልማት ስራዎች ሁሉ ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጠው ይገልጻሉ። ስራውን በክልሉ ባሉት ሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች ድረስ በማውረድ በየደረጃው ያሉ የወጣቶችና ስፖርት ቢሮዎች ከአስተዳዳሪዎችና የመሬት አስተዳደር ኃላፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ በመስጠት መግባባት ላይ እንዲደርሱ በማድረግ እየተከናወነ መሆኑን ይገልጻሉ።
በከተሞች አካባቢም በተመሳሳይ ከከንቲባዎችም ጭምር በመነጋገር ለስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ቅድሚያ እንዲሰጥ በመሰራቱ የተሻለ አፈጻጸም ላይ መደረሱን ነው ዳይሬክተሩ የሚጠቁሙት። ከሚጠበቀው በላይ በመስራት የተሻሉ ከሆኑት ዞኖች መካከል የምዕራብ ጎጃም ዞን ቀዳሚ ነው። በዞኑ የሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ሊባል በሚችልበት ሁኔታ 99ከመቶ የሚሆኑት የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ያላቸው ናቸው። በማዘውተሪያ ስፍራዎቹ ላይ ወጣቶች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ከማድረግም ባለፈ የተለያዩ ኃይማኖታዊ ክብረበዓሎች የሚከበሩበት በመሆኑ ህብረተሰቡም ቦታዎቹን አጥሮ እንክብካቤ ያደርግላቸዋል። ከዚህ ባሻገር በቀጣይ ቦታዎቹን የተሻለና ደረጃውን የጠበቀ የማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲሆኑ ነው የሚሰራው።
በአንጻሩ አንዳንድ ዞኖች ላይ በበቂ በልኩ ያልተሰራ መሆኑን መታዘብ ይቻላል። ከዚህ ውጪ ግን በዚህ ስራ ላይ የሚያጋጥመው ችግር ለስፖርት ማዘውተሪያ ሊሆኑ የማይችሉና የቦታ አቀማመጣቸውም ምቹነት የሌላቸውን ቦታዎች መስጠት ነው። በተለይ በአዊና በሌሎች አካባቢዎች ላይ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ለኢንቨስትመንት እና ለተለያዩ ግንባታዎች እንዲውሉ ሲደረግ ተስተውሏል። በምትክ የሚሰጠው ቦታ ደግሞ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ምቹ ያልሆኑ ናቸው። እነዚህን ቦታዎች ለማስተካከል ደግሞ የቢሮውም ሆነ የህብረተሰቡ አቅም ብቁ አለመሆኑ በስራው ላይ እንቅፋት መሆኑን ነው የሚያብራሩት።
የበሬ ግንባር የሚያክል ሜዳ ማግኘት አዳጋች በሚሆነባት የአዲስ አበባ ከተማ፤ ወጣቶች፣ አዋቂዎችና ስፖርተኞች በየመኪና መንገዱ ከተሽከርካሪዎች ጋር እየተጋፉ ስፖርት ለመስራት ይገደዳሉ። በከተማዋ የሚገኙት በጣት የሚቆጠሩ ስፍራዎችም ከሃይማኖታዊ በዓላት መከበሪያነታቸው ባሻገር፤ ታዳጊ ወጣቶችና ስፖርተኞች ህልማቸውን ለማሳካት አዋቂዎችም ጤናቸውን ለመጠበቅ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ተጨናንቀው ይስተዋላሉ። የአንድ ከተማ ማስተር ፕላን ሊያሟላ ከሚገባው መስፈርት መካከል አንዱና መሰረታዊው ጉዳይ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ቢሆንም፤ በሚፈለገው ልክ ትኩረት አይሰጣቸውም ነበር። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮም የነዋሪውን ቅሬታ ለመመለስ እንዲሁም ህብረተሰቡ በሚኖርበት፣ በሚማርበትና በሚሰራበት አካባቢ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሳተፍ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል።
በዚህም በየአካባቢው ያሉና በማስተር ፕላኑ ላይ የተቀመጡ ሜዳዎችን የይዞታ ማረጋገጫ እንዲያገኙ የማድረግ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ቢሮው ከጥርጊያ ሜዳ ደረጃቸውን እስከ ጠበቁት ትልልቅ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችም፤ ከፍተኛ ወጪ በማድረግ እድሳት፣ ጥገናና ግንባታዎችን እያከናወነ ነው። በተያዘው ዓመት ጥር ወር በወጣው ሪፖርት መሰረትም፤ በአጠቃላይ በከተማ አስተዳደሩ 633 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል ካርታ ያላቸው 568 ሲሆኑ፤ የሌላቸው ደግሞ 65 ናቸው። እነዚህ ስፍራዎች በሚፈለገው ልክ አገልግሎት እንዲሰጡ እንዲሁም ለተገልጋዮች ምቹ እንዲሆኑም ቢሮው 100 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ እየሰራ ይገኛል።

 

ኢትዮጵያዊያኑ በዩጂን ዳይመንድ ሊግ

 

በተያዘው ወር መጨረሻ በሚካሄደው የዩጂን ዳይመንድ ሊግ ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ታውቋል። በዓመታዊው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ሶስተኛውን ዙር የምታስተናግደው የአሜሪካዋ ዩጂን ከተማ ስትሆን፤ በዓለም ሻምፒዮናዎቹ ኬንያዊያን እንዲሁም በኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች መካከል ከፍተኛ ፉክክር እንደሚኖር ይጠበቃል። አማን ወጤ እና ወጣቱ አትሌት ሳሙኤል ተፈራን ጨምሮ በ1ሺ500ሜትር ፈጣን ሰዓት ያላቸው አትሌቶች በውድድሩ ላይ እንደሚካፈሉም ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በድረ ገጹ አስነብቧል። አብዛኛዎቹ አትሌቶች ከ3ደቂቃ ከ50ሰከንድ በታች የሆነ ምርጥ ሰዓት ያላቸው መሆኑም ፉክክሩን ይበልጥ አጓጊ ያደርገዋል።
ወጣቱ አትሌት ሳሙኤል ተፈራ ከሁለት ወራት በፊት በበርኒንግሃም በተካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና አሸናፊ መሆኑ የሚታወስ ነው። በወቅቱ የ18ዓመቱ ወጣት ርቀቱን ያጠናቀቀው 3:58.07 በሆነ ሰዓት ቢሆንም፤ አቅሙን በማጎልበት ውድድሩ ላይ ከፍተኛ ተፎካካሪ ሆኖ እንደሚገኝ ተስፋ ተጥሎበታል። አትሌቱ ከሌሎቹ አንጻር ያለው ፈጣን ሰዓት የዘገየ ቢሆንም በዚህ ውድድር ግን የተሻለ ፉክክር በማድረግ ፈጣን ሰዓት ያስመዘግባል በሚልም ይጠበቃል። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ባለክብረወሰን አትሌት አማን ወጤ በዚህ ርቀት ለአምስት ጊዜያት ባደረጋቸው ውድድሮች ሶስተኛ በመውጣት ጥንካሬውን ያስመሰከረ አትሌት ነው። አትሌቱ ከአራት ዓመታት በፊት ያስመዘገበው 3:48.60 የሆነ ሰዓትም የግሉ ፈጣን አለው፤ በዚህም ለኬንያዊያኑ አትሌቶች ፈተና እንደሚሆን ተገምቷል።
የዓለም ሻምፒዮናው ኢሊጃ ማናንጎይ እንዲሁም ያለፈው ዓመት የዳይመንድ ሊግ ሻምፒዮናው ቲሞቲ ቺሩዮት የውድድሩ ተሳታፊ መሆናቸው ፉክክሩን ይበልጥ ፈታኝ ያደርገዋል የሚል ግምት አሰጥቶታል። አትሌቶቹ በቅርቡ በተካሄደው የኮመን ዌልዝ ውድድር ላይ ተሳታፊ መሆናቸውም ለዳይመንድ ሊጉ ይበልጥ የሚያግዛቸው ሲሆን፤ ባለፈው ዓመት ዳይመንድ ሊግ በሞናኮ ተሳትፈው 3:28.80 እና 3:29.10 የሆነ የግላቸውን ምርጥ እና ተቀራራቢ ሰዓት አስመዝግበዋል።
ሌላኛው በርቀቱ ስኬታማ መሆን የቻለው ጅቡቲያዊው አትሌት አያልነህ ሱለይማንም በተመሳሳይ በውድድሩ የአሸናፊነት ቅድመ ግምቱን ካገኙት አትሌቶች መካከል አንዱ ነው። አትሌቱ ከአራት ዓመታት በፊት በአሜሪካ በተካሄደ ውድድር ላይ በነበረው ተሳትፎው 3:47.32 ሰዓት በማስመዝገብ የቦታው ክብረወሰን ባለቤት ነው። ሌላኛው ኬንያዊ አትሌት ሲላስ ኪፕላጋት ከአያልነህ ጋር በአሜሪካ ባደረገው ውድድር 56ማይክሮ ሰከንዶች ብቻ ተበልጦ ነበር የገባው። ይህም አትሌቶቹን የውድድሩ ከፍተኛ ተፎካካሪዎች ያደርጋቸዋል።

 

 

ሰላሳ ቀናት የቀሩት - የታላቁ የዓለም ዋንጫ ዝግጅት

 

የ88ዓመት ዕድሜ ባለጸጋው፤ ግን ደግሞ በየአራት ዓመቱ ተናፍቆ የሚመጣው ዓለም ዋንጫ ለ21ኛ ጊዜ ሊካሄድ ዛሬ 30 ቀናት ብቻ ቀርተውታል። ሩሲያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለምታካሄደው የእግር ኳስ ስፖርት ታላቁ ውድድር፤ ዝግጅቷን አጠናቅቃ እንግዶቿን ለመቀበል ተሰናድታለች። አውሮፓዊያኑን ጨምሮ በርካታ ሃገራትም በሩሲያ ላይ ባደረባቸው ጥርጣሬ እንደታጀቡ በግማሽ ልባቸው ወደ ሩሲያ ሊያቀኑ የመጨረሻ ምዕራፍ ዝግጅታቸው ላይ ይገኛሉ።
የዓለም መገናኛ ብዙሃንም ለአንድ ወር ያህል ትኩረታቸውን በሩሲያ ለማድረግ የሚገደዱ ሲሆን፤ በአካል ተገኝተው ከሚመለከቱት በሚሊዮን ከሚቆጠሩ ደጋፊዎች ባሻገር በቢሊዮን ለሚቆጠር ህዝብም ጨዋታዎችን ያስመለክታሉ።
በምዕራባዊያኑ ዘንድ ስሟ በበጎ የማይነሳው ሩሲያም ውድድሩን ከስፖርታዊ መድረክነቱ ባሻገር ለፖለቲካዊ ፍጆታ የምትጠቀምበት እንደመሆኑ ከፍተኛ ዝግጅት አድርጋበታለች። በዚህም እስካሁን ከታዩት የዓለም ዋንጫዎች ሁሉ ያማረና እንከን የለሽ ሆኖ እንደሚጠናቀቅም የማጠቃለያ ስራዎች ላይ ትገኛለች።
የፊፋው ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖም ከወራት በፊት ዝግጅቷን እንዳጠናቀቀችና የሚቀራት ጥቃቅን ስራዎች ብቻ መሆናቸውን፤ «ሩሲያ ዓለም ዋንጫውን ለማስተናገድ 99 በመቶ ዝግጁ ሆናለች፤ በታሰበው መልክም ስራዎቹ ተጠናቀዋል። ይህም መልካም ተሞክሮ ሲሆን፤ ወደሃገሪቷ የሚሄድ ማንኛውም ሰው በዚህ ደስተኛ ይሆናል» ሲሉ ነበር የገለጹት።
ለውድድሩ አዲስ የተገነቡና ነባር ስታዲየሞች በ13 ከተሞች የተዘጋጁ ሲሆን፤ ሃገሪቷ በአውሮፓ እና በእስያ አህጉሮች ከምትጋራው የመሬት ክፍሏ ለመጓጓዣ በእጅጉ እንዳይርቁ ሲባል ሁሉም ስታዲየሞች በእስያው ክፍል ይገኛሉ። ሉዢኒኪ የተሰኘው ስታዲየም የመክፈቻና መዝጊያ መርሃግብሮች ይስተናገዱበታል። ሩሲያ ከሳውዲ አረቢያ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን የሚያካሂዱትም በዚሁ ስታዲየም ነው።
ሌላኛው ደግሞ እአአ የ2014ቱን የክረምት ኦሊምፒክ እንዲሁም ያለፈውን ዓመት የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ያስተናገደው በሃገሪቷ ደቡባዊ ክፍል የሚገኘው የሶቺ ስታዲየም ነው። ስታዲየሙ አሁንም የዓለም ዋንጫን ከሚያስተናግዱት መካከል አንዱ ሲሆን፤ የፊፋው ፕሬዚዳንት በድጋሚ በዚህ ቦታ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ተገናኝተዋል። ከጉብኝቱ በኃላ በሰጡት አስተያየትም «ሃገራችሁ ሙሉ ለሙሉ ዝግጅቷን አጠናቃለች፤ የቀሩ ስራዎች ካሉም በቀሩት ጊዜያት ማጠቃለል ይገባል» ሲሉ ማረጋገጫውን ሰጥተዋል።
ፕሬዚዳንት ፑቲን በበኩላቸው «ኃላፊነታችን ምን እንደሆነ እናውቃለን፤ በትክክል መወጣት እንዳለብንም እንዲሁ። ለዝግጅቱ በሚፈለገው ልክም እየተጓዝን እንገኛለን» በማለት ነው ለዝግጅቱ የሰጡትን ቦታ ያመላከቱት። ጨዋታዎች የሚካሄዱባቸው ስታዲየሞች ለቡድኖቹም ሆነ ለደጋፊዎች ምቹ በሆነ መልኩ ተገንብተው መጠናቀቃቸውንም በመግለጫው ወቅት ማከላቸውንም የሮይተርስ መረጃ ያሳያል። ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች በተገናኙበት ወቅትም የመጀመሪያ እንደሆነ የተነገረለት የደጋፊዎችን ካርድ በየግላቸው ወስደዋል።
ዓለም ዋንጫው ላይ በተለያዩ መንገዶች የማስተባበሩንም ሆነ ሌሎች ስራዎችን የሚሰሩ በርካታ የበጎ ፈቃድ ሰራተኞችም በተጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ። 17ሺ የሚሆኑ በጎ ፈቃደኞች መመዝገባቸው የታወቀ ሲሆን፤ ከአራት ዓመታት በፊት ከተካሄደው የብራዚሉ የዓለም ዋንጫ በ2ሺ ብልጫ ያለውም ነው። ለዚሁ ስራ በቅድሚያ ማመልከቻቸውን ያስገቡት 176ሺ በጎ ፈቃደኞች ቢሆኑም ተቀባይነት ያገኙት ግን 17ሺዎቹ ብቻ ናቸው፤ ከእነዚህ መካከል 64በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።
ዓለም አቀፉን እግር ኳስ የሚያስተዳድረው ፊፋ የዳኝነት ስህተትን ለማረም በቪዲዮ የታገዘ እንዲሆንና ይኸውም በዓለም ዋንጫው በተግባር ላይ እንዲውል ማድረጉ የሚታወቅ ነው። ሩሲያ ግን ከዚህ በተጓዳኝ የየቡድኖቹ የህክምና ባለሙያዎችም በቪዲዮ ታግዘው እንዲሰሩ ማድረጓ ታውቋል። በተለይ የተጫዋቾችን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል በሜዳው አቅራቢያ የሚኖሩት ባለሙያዎቹ በዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ለተጫዋቾቻቸው በቶሎ ለመድረስ እንደሚረዳቸውም ታምኖበታል። ከዚህ ባሻገር ሃገሪቷ 200 የሚሆኑ የህክምና ባለሙያዎችን በስታዲየሞች አካባቢ ለሚፈጠሩ አደጋዎች እንዲሁም ድንገተኛ ጉዳቶች አሰልጥና አዘጋጅታለች።

ብርሃን ፈይሳ

 

Published in ስፖርት

ተመራማሪዎች በአንድ ወቅት ስድስት እናቶችን በአንድ ክፍል ውስጥ እንዲገኙ አደረጉ። ከሰባት ዓመት ያልበለጠ ዕድሜ ያሏቸውን ልጆቻቸውንም አንድ በአንድ ዓይናቸውን ሸፍነው እናቶቹ ወዳሉበት ክፍል መሯቸው። ከትንንሾቹ ሕፃናት ከፊሎቹ የእናቶቻቸውን ፊት እና ሌሎች የአካል ክፍሎች በመደባበስ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ የልብሶቻቸውን ጠረን በማሽተት የየራሳቸውን ለዩ። የሚገርመው ሕፃናቱ እናቶቻቸውን ለማግኘት በሚያደርጉት ፍለጋ ሁሉም እናቶች እንደራሳቸው ልጅ በማቀፍና ራሳቸውን በማሻሸት ሊያወዛግቧቸው ሞክረው ነበር። ነገር ግን አንዳቸውም ሳያመነቱ ነበር የመጀመሪያ ዓለማቸውን ያገኟት።
ምድራችን ለእኛ ለነዋሪዎቿ እንድትመች ሆና መፈጠሯ ለክርክር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። አየሯን መተንፈሳችን፣ በአካሏ ላይ መረማመዳችን፣ ውሃዋን መጠጣታችን፣ ከምታበቅለው መቋደሳችንና በስጦታዎቿ መገልገላችንም ለዚህ ምስክር ይሆናል። ከምድርም ከዓለምም በፊት ግን ፍጥረታትን ሁሉ አንድ ቋንቋ የሚያጋራ ሌላ ዓለም አለ፤ ይህ ዓለም ግን ከምድሪቷም ሆነ ከየትኛውም ጉዳይ ሊነጻጸር አይቻለውም። መፈጠሪያ፣ የወራት መኖሪያና እስትንፋስ ብቻም ሳይሆን የየትኛውም ፍላጎት መዳረሻ እናት መሆኗ ከምድሪቷ የማትነጻጸር ስጦታ ያደርጋታል። ታዲያ የትኛውም ፍጥረት ለመወለድ በቅቶ ከማህጸን ከወጣ በኋላም ሳይነገረው እናቱን የሚለይበት የተለየ ስሜት አለው።
የዚህን ስሜት ምክንያት ለማወቅም ሀሪ ሃርሎው የተሰኘው አሜሪካዊ የስነ-ልቦና ባለሙያና ተመራማሪ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ያደረገውን ሙከራ መመልከት ይገባል። አዲስ የተወለደችውን ሕፃን ጦጣ ከእናቷ ለይቶ በአንድ ክፍል ያስቀምጣታል፤ ከዚህ በኋላም በአንድ ወገን ከሚሞቅና ምቹ ከሆነ ጨርቅ በጦጣ ቅርጽ የተሠራ አሻንጉሊት በሌላው ደግሞ ከሽቦ የተበጀና ወተት የተሞላበት ጠርሙስ ያለው ሌላ ቅርጽ አስቀመጠ። እናቷን ያላየቻትና ከመወለዷ ወደ ቤተ-ሙከራው የተወሰደችው ጦጣ ግን ወተት የያዘውን ሳይሆን ከጨርቅ የተሠራውን የጦጣ ቅርጽ መርጣ ከጉያው ተገኘች። ይህም ለተመራማሪው፤ የእናትና ልጅ ግንኙነት ከወተት ጋር የተያያዘ ሳይሆን ከምቾት ጋር የተገናኘ መሆኑን ያመላከተ ሆነ። ይኸው ሙከራም እስከ አሁን ድረስ ከእናትነት ጋር በተያያዘ የሚነሳ ተምሳሌት ሆኗል።
ሳይንቲስቶቹ በተለያየ መንገድ በሚያደርጉት የጥናት ውጤት እናትነትን ሊገልጹት ይችላሉ፤ እውነቱ ግን እናት ከሙከራዎቹም ሆነ ከተግባር ይበልጥ የገዘፈች መሆኗ ነው። እናትነት መተኪያ የማይገኝለት የልጅ ምቾትና ተድላ ነው፤ ከየትኛውም ገንዘብ፣ ሀብትና ዕውቀት በላይ የሆነ ተሰጥኦም ነው። ሰውን ጨምሮ በየትኛውም ፍጥረት እናትነት ተመሳሳይ ስሜት ያለው ሲሆን፤ አምጣ በወለደችበት ቅጽበት ህመሟን ዘንግታ ለልጇ መንሰፍሰፏ የፍቅር አልፋ እና ኦሜጋነቷ ምስክር ነው። ፍቅር ስሜት በመሆኑ ሊለካም ሆነ ሊመዘን ባይችልም የትኛውም ፍቅር ግን የእናት ፍቅር ላይ ሊደርስ አይችልም። የስጋዋ ክፋይ፣ የደሟም ቅጂ ለሆነው ልጇ የምትሰስተውም ሆነ የምታሳንሰው ነገር ባለመኖሩ፤ ባለቅኔዎች፣ ጠቢባን ፈላስፎችና አዋቂዎች ሁሉ ብዙ ብለውላታል።
ይሁን እንጂ ስሜቱን ሊገልጽ የሚችል አንድም ቃል ሊያገኙ አልተቻላቸውም። አንድ ቀን ብቻ ለእርሷ መወከል ቢያንስም ትናንት ግን «የእናቶች ቀን» በሚል ስያሜ እናቶቻቸንን አስበን ውለናል። ይህ ቀን በአብዛኛዎቹ የዓለም ሃገራት በየካቲት እና በግንቦት ወራት የሚከበር ሲሆን፤ በዋናነት የመልካም ምኞት መግለጫ ካርዶችንና ስጦታዎችን ለእናቶች በማበርከት፣ ቤተሰቦች በአንድ በመሰባሰብ የጋራ ማዕድ ላይ በመገኘት፣ ከቤት ርቀው ያሉትም ለእናቶቻቸው ስልክ በመደወልና የጽሑፍ መልዕክ ቶችን በመላክ እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች ያከብሩታል። እኛ በምን መልኩ አከበርነው የሚለውን መልስ ለየራሳችን ትተን፤ ሃገራት ግን ቀኑን እንዴት ያከብሩታል የሚለውን በጥቂቱ እንመልከት።
በአሜሪካ እና በፈረንሳይ ለዕለቱ ታላቅ ቦታ ከሚሰጣቸው በዓላት መካከል አንዱ ሲሆን፤ ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ ሲከበር የኖረም ነው። በዚህ ዕለት ቤተሰቦች በተለይም ልጆች ቀኑን ሙሉ ከእናቶቻቸው ጋር ያሳልፋሉ፣ አበባ፣ ካርድ እና ቸኮሌቶችንም ያበረክቱላቸዋል። በመጨረሻም በቤታቸውም ሆነ በሆቴሎች ተሰባስበው የቤተሰብ እራት ይመገባሉ።
ከ16ኛው ክፍለዘመን ጀምሮ በየካቲት ወር ዕለቱን የማክበር ረጅም ልምድ ያላት እንግሊዝ ናት። በቀደመው ወቅት «የእናቶች ዕሁድ» በሚል በሚጠሩት በዚህ ቀን ቤተሰብ ተሰባስቦ በእምነት ቦታዎች በመገኘት ነበር የሚያከብረው። ከ20ኛው ክፍለዘመን ወዲህ ግን ቤተሰብ በአንድነት ተሰባስቦ ስጦታዎችን ለእናቶች በማበርከት ያሳልፉታል።
«የእናቶች ቀን»ን ማክበር በቻይናዊያኑ ዘንድ የቅርብ ጊዜ ልማድ ነው። የግንቦት ወር በገባ በሁለተኛው ዕሁድ የሚከበር ሲሆን፤ የአደባይ ክብረ በዓልም ነው። ከዚህ ባሻገር ግን ልጆች ለእናቶች ስጦታ ያበረክታሉ።
ዕለቱን በታላቅ ክብርና በልዩ ሁኔታ ከሚያከብሩት ሃገራት መካከል ሜክሲኮ ተጠቃሽ ናት። አከባበሩ ንጋት ላይ የሚጀምር ሲሆን፤ «ላ ማናኒታስ» በሚል ዝማሬ ታጅቦ፤ በተለያዩ ሬስቶራንቶች በመገኘትና ለዕለቱ የተዘጋጁ ምግቦችን በመመገብ እንዲሁም በሙዚቃዎች ደምቆ ይውላል።
ሩሲያም ዕለቱን በየካቲት ወር ከሚከበረው የሴቶች ቀን ጋር በማያያዝ የምታከብረው ሲሆን፤ ግብፅን ጨምሮ በበርካታ የአረብ ሃገራት ዕለቱ ብሄራዊ በዓል ተደርጎም ይታሰባል፡፡

ብርሃን ፈይሳ

Published in መዝናኛ

ትምህርት ለአንድ አገር ሀብት ብቻ ሳይሆን የእድገት መሰረት የሆነው የሰው ኃይል በዕውቀትና በክህሎት የማበለፀጊያ መንገድ ነው፡፡ በመሆኑም በአገሪቱ የሚሰጠው ትምህርት ተደራሽ ብቻ ሳይሆን ጥራት ያለውም እንዲሆን በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ በያዘው በጀት ዓመትም ይሄንኑ መሰረት ያደረጉ ተግባራት በእቅድ ተይዘው ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴርም ሰሞኑን የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈፃፀሙን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበ ሲሆን፤ ሚንስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ፣ በተለይም በዓመቱ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እየተተገበሩ የሚገኙ አምስት አበይት ተግባራት መኖራቸውን በሪፖርታቸው ገልፀዋል፡፡
ሚንስትሩ በሪፖርታቸው እንዳመለከቱት፤ እነዚህ ቅድሚያ የተሰጣቸው ተግባራት የዘርፉ የቀጣይ 15 ዓመታት ፍኖተ ካርታ ዝግጅት፣ የውጤታማ የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓት(ዴሊቬሮሎጅ)፣ የሁለተኛ ደረጃ የታሪክ ትምህርት መፃህፍትና ሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት፣ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ማሻሻያ መርሃ ግብርና የዘመነ ትውልድ ፕሮጀክት ናቸው፡፡ ለዛሬው እትማችንም የሚንስትሩን ሪፖርት መነሻ በማድረግ በተቋሙ ቅድሚያ የተሰጣቸው ሥራዎች በዘጠኝ ወሩ እንዴት ተፈፀሙ የሚለውን በሚከለተው መልኩ ይዘን ቀርበናል፡፡

የ15 ዓመታት ፍኖተ ካርታ ዝግጅት
በበጀት ዓመቱ በዘርፉ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እየተተገበሩ ከሚገኙ አበይት ተግባራት መካከል በመጀመሪያ ደረጃ የተቀመጠው አገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ የሚያስችል የትምህርትና ስልጠና የቀጣይ አስራ አምስት ዓመታት ዕቅድ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት ነው፡፡ በዚህም መሰረት የፍኖተ ካርታው ዝግጅት ያለፉትን ሃያ አምስት ዓመታት የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲዎች አተገባበር በመገምገምና ከ36 በላይ ከፍተኛ የትምህርት ባለሙያዎችንና ተመራማሪዎችን በማሳተፍ እየተሠራ ይገኛል፡፡
እስካሁን ባለው የዝግጅት ሂደት የሰነዶች ግምገማ ሥራ፣ የመስክ ሥራዎችና የዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ቅመራና ሪፖርት፣ የአጠቃላይ ወሳኝ ችግሮች ጥናት እንዲሁም ረቂቅ የማሻሻያ ሃሳቦች ጥንቅር ተጠናቋል፡፡ በቀጣይም ከመንግሥት በሚሰጠው አቅታጫ መሰረት ፍኖተ ካርታውን የመንደፍ፤ ባለ ድርሻዎችን በስፋትና በተለያዩ ስልቶች የማወያየትና የመጨረሻ ቅርፅ በማስያዝ አስፈላጊውን ሂደቶች በማሳለፍ ወደ ሥራ እንዲገባ የሚደረግ ይሆናል፡፡
የውጤታማ የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓት (ዴሊቬሮሎጅ)
ይህ ሥርዓት በአምስተኛው የትምህርት ዘርፍ ልማት ዕቅድ ውስጥ ከተቀመጡ 76 ግቦች መካከል እጅግ ወሳኝነት ያላቸውንና ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑትን ሦስቱን ግቦች በመለየት በውጤታማነት አሠራር ወደ ተግባር የተገባበት ነው፡፡ ከእነዚህ መካከልም የመጀመሪያው ግብ በአጠቃላይ ትምህርት ሁሉም ተማሪዎች በሁሉም አካባቢዎችና በሁሉም አገር አቀፍ የትምህርት ቅበላና ምዘና በሚሰጥባቸው የትምህርት ዓይነቶች ከአንደኛው የትምህርት ክፍል ወደ ሚቀጥለው ሲሸጋገሩ ሃምሳ በመቶና ከዚያ በላይ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የማድረግ አላማ ያለው ነው፡፡
ሁለተኛው ግብ ደግሞ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና በአጫጭርም ይሁን በረጅም ጊዜ የሚሰጡ ስልጠናዎችን በምዘና ያጠናቀቁ ዘጠና በመቶ በአንድ ዓመት ጊዜ ወደ ሥራ ገበያ እንዲቀላቀሉ ወይም ሥራ እንዲፈጥሩ የማድረግ አላማን ይዟል፡፡ በሦስተኛው ግብም በከፍተኛ ትምህርት ዘርፉ የትምህርት ጥራትንና አግባብነትን በማጎልበት 80 በመቶ የመጀመሪያ ዲግሪ መደበኛ ተመራቂዎች ወደ ሥራ ገበያ እንዲቀላቀሉ ወይም ሥራ እንዲፈጥሩ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡
የተቀመጡትን አላማዎች ለማሳካትም ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጀምሮ በየክልሉና በየተቋማቱ አስፈላጊ አደረጃጀቶች ተዘርግተዋል፡፡ ለመምህራንም የመወያያ ሰነድ በማዘጋጀትና ዝርዝር የማስፈፀሚያ ዕቅድ ወጥቷል፡፡ በዕቅዱ መሰረትም በሦስቱም ዘርፎች ዓለም አቀፍ አማካሪዎችን በማሳተፍ በሁሉም ተቋማት ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ አፈፃፀሙን በቅርብ የመደገፍ፣ የመከታተልና የመገምገም ሥራም እየተከናወነ ይገኛል፡፡
የታሪክ መጻህፍትና ሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት
በሁለተኛ ደረጃ የታሪክ መጻህፍትና ሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ረገድ የተያዙ ግቦችን ለማሳካት እስካሁን በተደረጉ ጥረቶች በበጀት ዓመቱ የ9ኛና የ11ኛ ክፍሎች የታሪክ መጻህፍት ዝግጅት ዘጠና በመቶ ተጠናቋል፡፡ የ10ኛ እና የ12ኛ ክፍሎች ደግሞ በዚህ ዓመት አጠናቆ ለ2012 ዓ.ም ዝግጅት የማድረግ ሥራ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ እየተሠራ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም ለሚዘጋጀው ሥርዓተ ትምህርት ምንጭ ሆኖ የሚያገለግል የኢትዮጵያ ህዝቦች ታሪክ የአገሪቱን ምሁራን፣ የሚመለከታቸውን ተቋማትና አካላት በማሳተፍ በአግባቡ ለማፃፍ የቢጋርና የማስፈፀሚያ ዕቅድ ቅድመ ዝግጅት ሥራ ተጠናቆ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ይገኛል፡፡
የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ማሻሻያ
ባለፉት ዓመታት በተለያዩ አካላት ተጠንተው ያለቁ ሦስት የጥናት ውጤቶችን መነሻ በማድረግ የማስተግበሪያ ዕቅድ በማዘጋጀት በሦስቱም ዘርፎች ገዥ መመሪያና ዕሴቶች ለማሻሻል ከ197 የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች፣ የብዙሃን ማህበራትና የዴሞክራሲ ተቋማት ግብዓቶችን የማሰባሰብ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሦስቱም ዘርፎች አደረጃጀቶችን የማስተካከልና የትምህርት ዓይነቱን መምህራን ምልመላና የስልጠና ሥርዓት የማሻሻል ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡
መርሃ ግብሩን ከመተግበር አኳያ በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፉ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ስልጠና ለ 1ሺ814 መምህራን የአሰልጣኞች ስልጠና በመስጠት እስካሁን ለ31ሺ 586 የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር መምህራን ስልጠናው ተሰጥቷል፡፡ ለተቀሩት 10ሽ 600 መምህራንም በደቡብ ክልል በተመረጡ የስልጠና ማዕከላት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት(ዩኒቨርሲቲዎች) ለሚያስተምሩ 749 የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት መምህራን ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል የማሰልጠኛ ማኑዋል ዝግጅት እና ሌሎችም ቅድመ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል፡፡ በቀጣይ ጥቂት ጊዜያት ውስጥም ስልጠናው በአንድ ማዕከል ሥር መሰጠት ይጀምራል፡፡
የዘመነ ትውልድ ዕቅድ ፕሮጀክት
የዘመነ ትውልድ ፕሮጀክት አገራት እስከ 2030 ባሉት ቀጣይ ሰላሳ ዓመታት ውስጥ እንዲያከናውኑት በመንግሥታቱ ድርጅት የትምህርት ኮሚሽን የተበሰረ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ዋነኛ ዓላማውም የሰብዓዊ ልማትን በዓለም ላይ ፍትሃዊ ለማድረግ ብቃት ያለውና ቴክኖሎጂን ለልማትና የዕድገት አቅም አድርጎ መጠቀም የሚችል ትውልድን መገንባት ነው፡፡ በአፍሪካም በዚህ መርሃ ግብር ሥር የታቀፉ አስራ አራት አገራት የተመረጡ ሲሆን፤ ኢትዮጵያን ቀዳሚ ተግባሪ ከሚሆኑ አገሮች አንዷ ለማድረግ የሚያስችሉ የሰነድ ዝግጅቶች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡
በቀጣይ ለተግባራቱ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች
አጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማስጠበቂያ ማዕቀፍን ለመተግበር የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል፣ በተለይም የመምህራንና የተቋማት አመራሮችን የምልመላና የስልጠና ሥርዓት ማሻሻልና እንዲሁም ሥርዓተ ትምህርቱን ለማሻሻል የተጀመሩ ሥራዎችን በማጠናቀቅ ወደ ተግባር ማስገባት የትኩረት አቅጣጫው አንዱ አካል ነው፡፡ የትምህርት ሥርዓቱን ውጤታማነት ለማረጋገጥ የተቀመጡ ተግባራትን በለውጥ ሠራዊት አደረጃጀት በመታገዝ መፈፀምም ቀጣይ ትኩረት የሚያሻው ሌላው ጉዳይ ሆኗል፡፡
በዚህ ረገድ በተለይም የማቋረጥንና የመድገም ምጣኔን መቀነስ፣ የመምህራን በሥራ ቦታ ላይ የመገኘት መጠንን መጨመር፣ ተግባር ተኮር ጎልማሶችና ልዩ ፍላጎት ትምህርት መርሃ ግብር አተገባበር ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡
በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ አሁን የተጀመረውን ከሴክተር መስሪያ ቤቶችና የልማት መርሃ ግብሮች ጋር በጋራ የማቀድና የመሥራት ጅምርን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገርም ትኩረት የሚሰጠው ሲሆን፤ በተለይ በዘርፉ ቴክኖሎጂን መቶ በመቶ የመቅዳት አቅም እንዲኖር በማብቃት፣ የተቋማት፣ የዩኒቨርሲቲንና የኢንዱስትሪ ትስስርን ማጠናከር ላይ ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል፡፡ ለዚህም ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት በንቅናቄ እንደሰሩ በማድረግና ውጤት ተኮር ሥርዓቱ ተጠናክሮ እንዲቀጠል ማድረግ ይገባል፡፡
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር፣ የጥናትና ምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ተልዕኮዎችን እንዲወጡ የአመራሩን የሥራ አመራር ክህሎት ማጎልበትና የተቋማትን አቅም የመገንባት ሥራዎች አጠናክሮ መተግበር ይገባል፡፡ የተጀመረውን የትምህርት ዘርፉ የቀጣይ 15 ዓመታት ፍኖተ ካርታ ማጠናቀቅና በሚቀጥለው ዓመት መጀመሪያ ላይ ወደ ተጨባጭ ተግባር ለመግባት የሚያስችሉ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ሆነው ተጠቅሰዋል፡፡

ይበል ካሳ

Published in ማህበራዊ

በየትኛውም አገር  ደረጃቸው ቢለያይም ከማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ችግሮች ማጋጠማቸው ያለንበት ክፍለዘመን ነባራዊ እውነታ ነው፡፡ በኢትዮጵያም እነዚሁ ችግሮች በየታሪክ ምዕራፉ ሲከሰቱ፤ በሕዝብ ጥረት ሲፈቱና ሲቀለበሱ ታይቷል፡ አሁንም ቢሆን በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ለመሆኑ የሚፈጠሩ ችግሮች መንስኤ ምን ይሆን? በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታስ እንዴት ይገለጻሉ? እነዚህን ችግሮች ከመፍታት አኳያ የሕዝብ ተሳትፎ ምን ይመስላል? በቀጣይስ ለሚፈጠሩ ችግሮች ሕዝቡን እንዴት የመፍትሄ አካል ማድረግ ይገባል? በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የፖለቲካ ዘርፍ ምሑራንን አስተያየት ይዘን ቀርበናል፡፡

የሚፈጠሩ ችግሮችና መንስኤዎቻቸው
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ረዳት ፕሮፌሰር የማነ ዘርዓይ እንደሚናገሩት፤ አገር የሚባለው መንግሥት፣ ግዛትና ሕዝብን ያካተተ አካል ነው፡፡ እነዚህ ራሳቸውን የቻሉና ሉዓላዊ ናቸው፡፡ የአገር ዋና መገለጫውም የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቱ ነው፡፡ እነዚህ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶች ደግሞ አንደኛ በአገር ውስጥ በሕዝብ ለሕዝብ ወይም ሕዝብ ከመንግሥት ጋር በሚኖራቸው መስተጋብር፤ ሁለተኛ በሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ አገራት መካከል የሚኖር የመንግሥት ለመንግሥት ወይም በሕዝብ ለሕዝብ ትብብሮች የሚገለጹ ናቸው፡፡
በዚህ መልኩ በውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶች ደግሞ አንድም ግንኙነቱን የሚያጠናክር ውጤት የሚገኝባቸው ሲሆን፤ በአገር ውስጥ የሚኖረው የሕዝብ ለሕዝብም ሆነ የመንግሥትና የሕዝብ ግንኙነት በዛች አገር ውስጥ ለሚኖረው ሁለንተናዊ ተግባር ውጤታማነት ያግዛል፡፡ በአገራት መካከል የሚፈጠረው ትብብርም ለዚሁ ተግባር ደጋፊ ይሆናል፡፡ ሁለተኛም በውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖረው ግንኙነት በተለያየ ምክንያት አንዱ በአንዱ ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥርና ጉዳት የሚያመጣ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ይህ ሲሆን በውስጥ በሕዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት ይሻክራል፤ ሕዝብና መንግሥትንም ወደ አለመተማመን ይወስዳል፤ የውጭው ተጽዕኖም ለውስጡ ችግር መባባስ ድርሻ ይኖረዋል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር የማነ እንደሚናገሩት፤ በአገር ውስጥም ሆነ በአገራት መካከል የሚኖሩ ግንኙነቶች በአንድ አገር ውስጥ ለሚፈጠር ሰላምና መረጋጋት ብሎም ልማት አጋዥ የመሆናቸውን ያክል፤ የግንኙነቶቹ በተለያየ መልኩ አሉታዊ ሁኔታ ውስጥ መውደቅ በዛች አገር ውስጥ ለሚኖረው የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶች ችግር ላይ መውደቅ ምክንያት ይሆናሉ፡፡ ለዚህ ችግር ከሚዳርጉ ጉዳዮች አንዱ በሕዝብና መንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት ሲሆን፤ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያለው አካል ለሕዝቡ መስጠትና ማድረስ የሚገባውን አገልግሎት ሲዘነጋ፣ ለመልካም አስተዳደርና አሠራር ብልሹነት ሲጋለጥ፣ ሥልጣንን አለአግባብ ሲጠቀም ሕዝብ ስለሚበደል በሕዝብና መንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት ስለሚያሻክረው በአንድ አገር ውስጥ ለሚፈጠረው የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግር መነሻ ይሆናል፡፡
ሁለተኛም አንድ አገር የተለያዩ ሕዝቦች መገኛ እንደመሆኑ በታሪክም ሆነ ሌሎች የቀደሙና ያሉ ሁነቶች ምክንያት በሕዝቦች መካከል አለመተማመንና መጠራጠር ሊፈጠር፤ ወደ ግጭትም ሊያመራ ይችላል፡፡ ይህም በአንድ አገር ውስጥ ለሚኖር ሰላም መደፍረስና ልማት መደናቀፍ ምክንያት ይሆናል፡፡ ከዚህ ባለፈ አንድ አገር ከዓለም ተነጥላ መኖር አይቻላትም፤ ለዚህም ከተለያዩ አገራት በተለያዩ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር የትብብር ግንኙነት ትፈጥራለች፡፡ ሆኖም በአገራት መካከል የሚኖር ግንኙነት በተለያዩ የጥቅም ምክንያቶች መሻከር በውጫዊ ገጽታው የሚያበቃ ሳይሆን በአገር ውስጥ በሚኖረው የውስጥ ሰላምና ልማት ላይ አሉታዊ ጥላን በማጥላት በአገር ውስጥ ለሚኖረው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች መነሻ ሊሆን ይችላል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ምሑር የሆኑት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ በተለይ በአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ በሚወጡበት ወቅት ብዙ ተስፋ ያደረጉ ነበሩ፡፡ ሰላምና መረጋጋትን ያመጣሉ፣ ዴሞክራሲን ያሰፍናሉ፣ የሰብዓዊ መብቶችንም ያከብራሉ ተብሎ ተስፋ የተጣለባቸው ነፃ አውጪ ታጋዮችና ፓርቲዎችም የሚፈለገውን ውጤት ሳያመጡ፤ ውጤቱ የተገላቢጦሽ ሆኗል፡፡ ለምሳሌ፣ የዓለም ባንክና የአይ.ኤም.ኤፍ ስትራክቸራል አሰስመንት ፕሮግራም በመጣ ጊዜ የሰውን ኑሮ ቀውስ ውስጥ ስለከተተው ወደ 40 የመንግሥት ግልበጣዎች ነው የተካሄዱት፡፡ በመንግሥት ኃላፊነት ላይ የተቀመጡ ሰዎች አገርን ያለ አግባብ መዝረፍ በመበራከቱ በተፈጠሩ ችግሮችም በአፍሪካ ውስጥ ከ110 በላይ የመፈንቅለ መንግሥት ተካሂዷል፡፡

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ


ከዚህ ባሻገር ግን ሰብዓዊ መብቶች መገፈፋቸ ውና የማህበራዊ አገልግሎቶች ከመዳከም አልፈው መሞታቸው ለተከሰቱት 110 የመንግሥት ግልበጣዎች ምክንያቶች ነበሩ፡፡ የመንግሥት ግልበጣን ለማከናወን ደግሞ የወታደሩ ክፍል ሁል ጊዜ ዕድል ያለው ነው፡፡ እንደመሆኑም፤ ምንም እንኳን ኋላ ላይ መልሰው አንድነት ቢፈጥሩም የሕዝብ ቅሬታን ጠብቀው ለግልበጣው ይጠቀሙበታል፡፡ በዚህ መልኩ የሚመጡ ድርጅቶችም ናቸው የሃይማኖት፣ የብሔርና ሌሎች ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጫናዎች በማሳደር ሕዝቡን የሚበድሉት፡፡ ይህ ደግሞ ሕዝቦች ለእርስ በእርስ አለመተማመንና ግጭት እንዲዳረጉ፤ ካልሆነም ለለውጥ እንዲያምጹ ምክንያት ይሆናል፡፡
በተመሳሳይ ጥቂት ሰዎች ሀብታም እየሆኑ ሕዝቡ በሙሉ ሲደኸይ በኢኮኖሚ መስኩ የሚከሰት ችግር ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በአፍሪካ አገሮች በኢኮኖሚውም መስክ ሕዝቡ ተሳትፎ ስለሌለው የሚፈለገውን የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር አልተቻለም፡፡ ለምሳሌ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 24 ትሪሊዬን የሚገመት ሀብት ቢኖራትም ሕዝቡ ግን በድህነት አረንቋ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ሲያጣና ሲነፈግ ለአመጽ ይነሳል፤ ችግሮችም ይፈጠራሉ፡፡
የችግሮቹ ገጽታ - በኢትዮጵያ
ረዳት ፕሮፌሰር የማነ እንደሚሉት፤ እነዚህ አገራዊና ዓለምአቀፋዊ ጉዳዮች አሁን ላይ በኢትዮጵያ ለሚስተዋሉት ብቻ ሳይሆን ቀደም ሲል ለነበሩት የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግር ምክንያት ሲሆኑ ተስተውሏል፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የሥልጣኔ ታሪክ ያላት ሰፊ አገር ናት፡፡ የረዥም ታሪክ ባለቤት ብቻም ሳይሆን ከሦስት ሺህ ዓመት በላይ ዘመናዊ የፖለቲካ አደረጃጀትና በዚህ ሥርዓት የሚመራ ሕዝብ ያላትም ናት፡፡ ዛሬም ሰፊ ቁጥር ያለው ሕዝብ፣ የተፈጥሮ ሀብት ያላት፤ ቅኝ ሳትገዛ የቆየች እና በርካታ ዓለምአቀፍ ጦርነቶችን ያደረገች አገር ናት፡፡ በውስጧም የጭቆና ታሪክ አቅፋ የቆየች ሲሆን፤ ይህ የጭቆና ታሪኳም አሁን ላለው የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግር አሻራውን ጥሏል፡፡
ለአብነት በ1960ዎቹና 70ዎቹ የነበረው ሁኔታ ቀደም ሲል አገሪቱ በነበራት ትልቅ ገጽታ ላይ ጥላ እንዲያጠላ ያደረገ ነበር፡፡ ይሄን ታሪክ ለመቀልበስ ባለፉት አርባ እና ሃምሳ ዓመታት ብዙ ትግል ተደርጓል፡፡ የዚህ ውጤት አዎንታዊ ቢሆንም የትግል ሂደቱ አሉታዊ ጎንም ነበረው፡፡ በመሆኑም እነዚህ ታሪካዊ ዳራዎች አሉታዊ አስተዋጽዖ በማበርከት አሁን ላይ ለተደረሰበት ችግር ድርሻ አላቸው፡፡ አሁን ያለው ትውልድም ከእነዚህ የታሪክ ሁነቶች ሙሉ ለሙሉ ተላቋል ማለትም አይቻልም፡፡ እነዚህን መጥፎ ታሪኮች በአግባቡ መፍታት ካልተቻለ፤ ወይም የአፈታት ሂደቱ ቀርፋፋ ከሆነ ወጣቱ አሁን ላለበት ብቻ ሳይሆን ወደፊት ለሚኖረውም የራሳቸውን መጥፎ አሻራ ያሳርፉበታል፤ የበለጠም የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጽዕኖም ያሳድራሉ፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ የአገሪቱ ፖለቲካዊና መልከዓ ምድራዊ ሁኔታ ለውስጣዊ ችግሯ የራሱ አስተዋጽዖ አለው፡፡ ምንም እንኳን አሁን ላይ ኢትዮጵያ ያለችበት ጂኦ-ፖለቲካል ምህዳሯ ጥሩ የሚባል ቢሆንም፤ ይህ ብቻውን የውጫዊ ተጽዕኖውን ይቀንሰዋል ማለት አይቻልም፡፡ በውስጥ ያለውን በአግባቡና በጥንቃቄ ካልተያዘ ከውሃ ሀብቷና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶቿ ጋር በተያያዘም የበርካታ አገራትን ትኩረት የያዘች ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሌሎቹ በአሉታ እንዲመለከቱ ማድረጉ አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህ በዘለለም የአክራሪነትና ሽብርተኝነት እንቅስቃሴዎችም ትኩረት የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በተለይ ባለፉት 26 ዓመታት ያራመደችው የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ በመጠኑ ውጤት ማሳየት ጀምሯል፡፡ ይህ ደግሞ አዎንታዊ ጎን እንዳለው ሁሉ በተቃራኒውም አገሪቱ በአንዳንድ አገሮች በጥርጣሬ እንድትታይ የሚያደርጋት ነው፡፡
በጥቅሉ ሲታይ ግን የታሪክ ገጽታው ያለፈ ነው፤ ወደኋላ ተሄዶ ሊሰራ አይችልም፡፡ የውጭ ተጽዕኖውም ውጫዊ ምክንያት ነው፡፡ በመሆኑም አሁን ማድረግ የሚቻለው አንድም፣ የታሪኩ አሉታዊ ገጽታ መጥፎ ስዕል እንዳይፈጥር መስራት ሲሆን፤ ሁለተኛም የውጭ ኃይሎች እጃቸውን ለማስገባት ዕድል የሚሰጡ ውስጣዊ ጉዳዮች ላይ በአግባቡ መስራት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሕዝቡን፣ መንግሥትን፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን፣ መገናኛ ብዙኃንንና ሲቪክ ማርበራትን ባጠቃላይ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚመለከት ሥራ እንደመሆኑ፤ ሁሉም የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣትና የድርሻውን ማበርከት ይኖርበታል፡፡
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ለየት የሚያደርገው ግዛትን ለማስፋፋት የተደረጉ ጦርነቶች ካልሆኑ በስተቀር አንድ ብሔር የሌላ ብሔር ዘር ለማጥፋት ብሎ የተነሳበትና ጦርነት ያካሄደበት ታሪክ አለመኖሩ ነው፡፡ ከዚህ በዘለለ ግን የኢትዮጵያም ሕዝቦች ከንጉሣውያኑ ጊዜ ጀምሮ ቅሬታቸውን የሚያነሱበት፤ በትግልም ለጥያቄ ዎቻቸው ምላሽ ያገኙበት ተደጋጋሚ የታሪክ ምዕራፎች አሏቸው፡፡ ለምሳሌ በንጉሣውያኑ ዘመንም ጥቂት ሰዎች የአገሪቱን ሀብት ይዘው የሚንቀሳቀ ሱበት፤ ሕዝቡንም እንደ ሁለተኛ ዜጋ የሚመለከ ቱበት ሂደት ነበረ፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው የቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሲያነሱ የነበረው የብሔር ብሔረሰቦች መብት ጥያቄ በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ ተሳትፎ የመብት ጥያቄ አካል ነበር፡፡ የመሬት ላራሹ ጥያቄም የመሬት ሀብቱ በጥቂት ግለሰቦች የተያዘበትን፤ ሰፊው ሕዝብ ግን የምርቱን ሲሶ እየከፈለ የሚኖርበትን የኢኮኖሚ ምዝበራ ለመቀልበስ ነበር፡፡ በ1966 የነበረው አብዮትም በወቅቱ ያልተመለሱ የመሬት፣ የእኩልነትና የማንነት ጥያቄዎችን መሠረት ያደረገ ነበር፡፡
ከዚያም በኋላ የመጣው የማርክሲዝም ሌኒንዝም አስተሳሰብ ግፊትም አገሪቱን ከችግር ያወጣ ሳይሆን ወደችግር ያስገባት፤ ይልቁንም ከቀደመው ተለይቶ የማይታይ ነበር፡፡ በተለይም ከባህል፣ ከቋንቋና ማንነት ጋር የተያያዙ የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄዎች በሰፊው የሚነሳበትም ነበር፡፡ ይሄም ለተመሳሳይ የሥርዓት ለውጥ ያደረሰ ትግል የተከናወነበት ሲሆን፤ የብሔር ብሔረሰቦች የማንነትና የእኩልነት ጥያቄም በሕገ መንግሥት ጭምር ለመቀረጽ በቅቷል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የብሔር ብሔረሰቦች መብት የራስን ዕድል በራስ እስከመወሰን የተሰጠው ድንጋጌ የፖለቲካ ፓርቲ ኃላፊዎች ብቻ ተጠቃሚ የሚሆኑበትና አገርን በሙስና ችግር ውስጥ የሚከቱበት እየሆነ መጣ፡፡ አሁን ላይ ያሉ ችግሮችም በዚህ መልክ የሚታዩ ናቸው፡፡
እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገለጻ፤ አሁን ላይ ኢትዮጵያ በመሠረተ ልማት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡ ኢኮኖሚዋም እያደገ ነው፡፡ ይህ እንዳለ ቢሆንም የሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዋና የሕዝቡ በደሎች ናቸው፡፡ በተለይ በወረዳ ደረጃ የሚመደቡ ኃላፊዎች ያለምንም ገደብ ሕዝቡን ሲዘርፉና ሰብዓዊ መብቱን ሲገፉት እንደነበር ነው የሚነሳው፡፡ ከዚህ ባለፈም ከየዩኒቨርሲቲውና ከሙያ ተቋማት የሚመረቁ ወደ 600ሺ ተማሪዎች ሥራ ከማግኘት ጋር በተያያዘ በሚፈጠርባቸው ተስፋ የማጣት ስሜት በቀላሉ ወደ ጽንፈኝነት የመቀየር አዝማሚያ አለ፡፡ በአገሪቱ ሲከሰት ለነበረው ችግርም ከፖለቲካዊ ችግሩ ባለፈ የዚሁ የወጣቶች ሥራ አጥነት ችግር ነበር፡፡
የሕዝብ ተሳትፎና የመፍትሄ አካልነት
ረዳት ፕሮፌሰር የማነ እንደሚሉት? የሕዝብ ተሳትፎ በተመለከተ መንግሥት እንዴት ነው ሕዝቡን እየመራ ያለው? ተቋማዊ ሕጎችስ አሉን? እነዚህ ሕጎችስ ሕዝቡ መክሮባቸውና አውቋቸው ወደሥራ የገቡ ናቸውን? የሚሉት ጉዳዮች መታየት ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሁነቶች የመንግሥትን ተጠያቂነትም ሆነ የሕዝብን ተሳትፎ ከማረጋገጥ አኳያ የጎላ ሚና አላቸው፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ ሕዝቡ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮቹ ላይ ከመሳተፍ አኳያ ጅምሮች አሉ፡፡ ሆኖም ተሳትፎውም ሆነ አሳታፊነቱ ዘላቂና ቀጣይነት ባለው መልኩ እየተከናወነ አይደለም፡፡
ምክንያቱም የሕዝቡ ተሳትፎ በሕግ ላይ ሳይሆን በፖለቲካ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ፤ የፖለቲካ ሁኔታውን ተከትሎ ያዝ ለቀቅ፤ ሞቅ ቀዝቀዝ እያለ የሚሄድ ነው፡፡ የሕዝብ ተሳትፎ ደግሞ ሕግ ላይ ካልተመሰረተ በቀር ወጥነት ባለው መልኩ በሁሉም ቦታና በሁሉም ጉዳይ ተሳታፊ ለማድረግ ያስቸግራል፡፡ ይሄም ዜጎች እኩል እንዳይታዩ፣ በሕግ ፊትም እኩል እንዳይዳኙ፣ የፍትሃዊነትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን እንዲያነሱ፣ እንዲሁም የመንግሥት አካል ተጠያቂነት እንዳይኖር ያደርጋል፡፡
እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገለጻ ደግሞ፤ ችግሮችን ለማቃለል ሕዝብን አሳትፎ መስራት ተገቢ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ሁኔታ ግን በሕገ መንግሥቱ ውይይት ላይ ተሳተፏል ከሚባለው ውጪ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሕዝብ ተሳትፎ የለም፡፡ ምክንያቱም እስካሁን በነበረው ሁኔታ የሕዝቡን ተሳትፎ ሳይሆን ሲያራምዱ የነበረው ሕዝቡ አዳማጭ ነው የተደረገው፡፡ ሕዝቡም የራሱን ዕድል በራሱ የሚወስንበትን ሕገ መንግሥታዊ መብት ሲተገበር አልታየም፡፡ ይልቁንም የመንግሥት ኃላፊዎች ሕዝቡጋ እየሄዱ ሲያስቸግሩት ከመስተዋል ባለፈ ለተሳትፎውና ተጠቃሚነቱ ከጅምላ ልፈፋ የዘለለ ከልብ አልተሰራም፡፡
የሕዝብ ተሳትፎን ለማረጋገጥ የሚቻለው አንድም ሕዝቡ የሚያምናቸው፣ የሚወዳቸውና ያገለግሉኛል ብሎ የሚያስባቸው ሰዎች መምረጥ ሲችል ነው፡፡ ከዚህ አኳያም የዴሞክራሲ ባህል ባልዳበረበት ሁኔታ ዝም ብሎ ምርጫ ስለተካሄደ ብቻ ሕዝቡ ተቀብሏል ማለቱ በራሱ ችግር ስላለው የዴሞክራሲ ባህሉን ማዳበር ይገባል፡፡ ምክንያቱም ሕዝብ ተሳትፏል ሲባል ሕዝቡ በፖለቲካ ውሳኔ ውስጥ መሳተፍ ይኖርበታል፤ በኢኮኖሚውና በማህበራዊ ልማት ውስጥም መሳተፍ ይገባዋል፡፡ ይህ ደግሞ ዝም ብሎ በጅምላ ተጠርቶ በጅምላ የሚሳተፍበት ሂደት መሆን የለበትም፡፡
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ እንደሚናገሩት፤ እነዚህ ሕዝቦች ትምህርት ሳይስፋፋና መንግሥት ሳይቋቋም ጀምሮ ይህችን አገር እንዴት በሰላም ጠብቀው አኖሯት? በዚህ ሂደትስ የሃይማኖት፣ የባህልና ሌሎች ማህበራዊ ተቋማትስ ሚና ምን ነበር? የሚለውን አውቆ ለመጠቀምና የሕዝቡን ተሳትፎ ለማረጋገጥ ሕዝቡ አምኖና አውቆ በህሊናው ተመርቶ እንዲሳተፍ ማድረግ ይገባል፡፡ ምክንያቱም አንድ ቄስ ወይም ኢማም የሚናገረው ቃል፤ ካድሬው ከሚናገረው በላይ በሕዝቡ ዘንድ የመስረጽ፣ ፈቃዳዊ ተቀባይነት የማግኘትም አቅም አለው፡፡
ዛሬ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በየክልሉ እየሄዱ የሕዝቡን ችግር የሚያዳምጡትና እንዴትስ መፈታት አለበት የሚለውን ከሕዝቡ ጋር ለመወያየት ያስገደዳቸው፤ በእስካሁኑ ሂደት ሕዝቡ የመብቱ ተጠቃሚ ሆኖ እንዲሳተፍ ባለመደረጉ ነው፡፡ አሁንም አገሪቱም ሆነች ሕዝቡ መረጋጋት የቻለው በዚሁ በእርሳቸው ንግግር ያውም በመጀመሪያው ቀን ንግግራቸው ባሳደረው ተስፋ ነው፡፡
ቀጣይ ሕዝቡን ለማሳተፍና የመፍትሄ አካል ለማድረግ
ረዳት ፕሮፌሰር የማነ እንደሚሉት፤ በማህ በራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሕግን መሠረት አድርጎ የሕዝቡ አለመሳተፍ ደግሞ በዋናነት የመልካም አስተዳደር ችግር ሕዝቡ ላይ እንዲጫን ያደርጋል፡፡ ይህ መልካም አስተዳደር ደግሞ ዝም ብሎ የሚመጣ ሳይሆን መሠረቱ ዴሞክራሲ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ያሉ መዋቅሮች በትክክል የሕዝብን ሉዓላዊነት የሚያንጸባርቁ መሆን አለባቸው፡፡ የሕዝብ ሉዓላዊነት የሚረጋገጠው ደግሞ የሕዝብ ተወካይ የሆኑ ምክር ቤቶች በትክክለኛ ምርጫ የመጡ ሲሆኑ እና ሲጠናከሩ ነው፡፡
ከዚህ ባለፈም እነዚህን ተቋማት የሚያግዙ እንደ ምርጫ ቦርድን፣ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና እንባ ጠባቂ፤ የመገናኛ ብዙኃን፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎችና ማህበራዊ ተቋማት መጠናከር የሕዝብን ተሳትፎ ለማረጋገጥ የሚያግዙ ናቸው፡፡ በመሆኑም የሕዝብ ተሳትፎን ማጠናከር የሚቻለው በዚህ መልኩ የተለያዩ አካላትን በማጠናከርና ሕዝቡም በቀጥታም ሆነ በተወካይ እንዲሳተፍ ሲደረግ እንደመሆኑ፤ በተለያዩ ምክንያቶች የሚነሱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን የመፍታቱ ሂደት የሕዝብ ተሳትፎን በእጅጉ የሚፈልግ መሆኑን ተገንዝቦ በዚሁ ልክ ሊሰራ ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን የሚፈለገው ውጤት ይገኛል፡፡
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ አሁን በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግርና ሕዝብን የማነጋገር ሂደት ሕዝቡ ትልቅ ተስፋ አሳድሯል፡፡ ሕዝቡም ብዙ ውጤቶችን ይጠብቃል፡፡ ይህ የሚሳካው ግን በእርሳቸው ብቻ ሳይሆን የሁሉንም አካልና የፓርቲውን ሙሉ ድጋፍ ሲያገኝ ነው፡፡ ሥርዓቱም የሕዝብ መሠረት ሊያዳብር የሚችለው የሕዝቡን ተሳትፎ ማጎልበት ሲችል ነው፡፡ ለምን ቢባል፣ ንጉሡ ሲወርዱ ሕዝብ ለምን አላለም፤ በተመሳሳይ ደርግ ሲወድቅ ማንም ሕዝብ ለምን ወደቀ አላለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ እሰየሁ ነው ያለው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሥርዓቶች የሕዝብ መሠረት አልነበራቸውም፡፡ አሁንም ይሄን ተገንዝቦ መስራት ለችግሮች ሁሉ መፍትሄ የሆነውን ሕዝብ ለማሳተፍና ችግሮችን ለማቃለል ያግዛል፡፡
በዚህ ረገድ የሕዝቡን ተሳትፎ ለማሳደግ የኅብረተሰቡን ባህል፣ እምነት፣ ሥነልቦናና አካባቢያዊ ሁኔታ በጥናት ታግዞ በአግባቡ መለየት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ሕዝቡን እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ መድረስና ማሳተፍ ተገቢ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ፣ በአንዳንድ ቦታ ሕብዙ በአባ ገዳ የሚተዳደር ሆኗል፤ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ የጎሳ ኃላፊዎች ሊያስተዳድሩት ይችላሉ፡፡ በመሆኑም የሕዝብ ተሳትፎ እንደየ ኅብረተሰቡ አካባቢና ቀዬ የሚወሰን እንጂ ለመላው አገሪቱ አንድ ቀመር ወጥቶ እንዲሳተፍ የሚደረግበት አይደለም፡፡
እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኒስ አባባል፤ በካድሬዎች የተለመዱ ቃላት “ኪራይ ሰብሳቢ”፣ “አብዮታዊና ልማታዊ መንግሥት”፣ ወዘተ እያሉ ሕዝቡ በማያውቀውና በማይገባው ቋንቋ ከማዳረቅ ይልቅ፣ ለሕዝቡ ቅርብ በሆኑት የሃይማኖት አባቶች፣ የባህል መሪዎችና ሌሎች ማህበራዊ ተቋማት አማካኝነት ሕዝቡ በሚያውቀው ቋንቋ አስረድቶና አሳምኖ ማሳተፍ ይገባል፡፡ የሕዝቡ ሃሳብ የሚንሸራሸርበት ዕድል እንዲኖርም ተፎካካሪ ፓርቲን በማጠናከር ጠንካራ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ መደገፍ፤ ሕዝቡም ለሰላማዊ የፓርቲ የሥልጣን ሽግግር መሳካት ግንዛቤ እንዲይዝ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የሲቪክ ማህበራትን ሚና ማሳደግ፤ ሚዲያውም በሚዲያው ሕግ እስከሰራ ድረስ በየምክንያቱ ከማስፈራራትና ከማሰር ተቆጥቦ የሕዝቡን ሀሳብ እንዲያራምድ ማገዝ፤ ችግሮችን እያጠኑ መንግሥት ከሕዝብ ጋር ተባብሮና ተደጋግፎ እንዲጓዝ የሚያስችሉ አሠራሮችንም መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መልኩ የሕዝቡን ፍላጎትና ስሜት ለይቶ ማሳተፍ ከተቻለ ሕዝብን አሳትፎ የማይፈታ ችግር ባለመኖሩ የሚፈጠሩ ችግሮችን ማቃለል፤ የሚፈለገውን አገራዊ ውጤትም ማምጣት ይቻላል፡፡

ወንድወሰን ሽመልስ

Published in ፖለቲካ

ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ለምግብ እጦት ይዳረጋሉ፡፡ የምግብ እጦት ደግሞ አንድም ጊዜያዊ ሆኖ፤ ካልሆነም ስር የሰደደ ሆኖ ሊከሰት ይችላል፡፡ ስር የሰደደ ሲባል የቤተሰቡ ጥሪት በጣም የተመናመነና ከድህነት ወለል ሲገኝ ነው፡፡ በአንፃሩ ጊዜያዊ ችግር ደግሞ በተፈጥሮም ይሁን በሰው ሰራሽ አደጋ ምክንያት በሚደርሱ ችግሮች የሚፈጠር የምግብ እጦት ነው፡፡
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት የማህበራዊ ነክ ዓላማዎች በሚዘረዝረው _አንቀጽ 90 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ እንደተመላከተው፤ _የአገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን ሁሉም ኢትዮጵያዊ የትምህርት፣ የጤና አገልግሎት፣ የንፁህ ውሃ፣ የመኖሪያ፣ የምግብና የማኅበራዊ ዋስትና ሊኖረው እንደሚገባ በግልጽ ደንግጓል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 41 ንዑስ አንቀጽ 5 መሠረት መንግሥት የአካልና የአዕምሮ ጉዳተኞችን፣ አረጋውያንንና ያለ ወላጅ ወይም ያለ አሳዳጊ የቀሩ ሕፃናትን ለማቋቋምና ለመርዳት የአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም በፈቀደው ደረጃ እንክብካቤ እንደሚያደርግ አስቀምጧል፡፡ በንዑስ አንቀጽ 6 ለሥራ አጦችና ችግረኞች ሥራ ለመፍጠር የሚያስችል ፖሊሲ በመቅረፅ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶችን ማካሄድ፣ በንዑስ አንቀጽ 7 ለዜጎች የሥራ ዕድሎች እንዲስፋፉ መንግሥት አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባው አስፍሯል፡፡
በተመሳሳይ በአንቀጽ 43 ንዑስ አንቀጽ 4 ላይም የመንግስት የልማት እንቅስቃሴ ዓላማ የዜጎችን ዕድገትና መሠረታዊ ፍላጎቶች ማሟላት እንደሆነም ያስቀምጣል፡፡ በጥቅሉ የሕገ መንግሥቱ በኢኮኖሚ ልማት መሠረታዊ ትኩረቱ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዋስትና ማረጋገጥ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን፣ ከዚህ አንፃር የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ጉዳይ ሕገ መንግሥታችን ከአቅም ጋር እየተገናዘበ መሟላት ያለበት መብት መሆኑን በግልጽ አስፍሯል፡፡ ይሄን መነሻ በማድረግ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የምግብ ዋስትና ስትራቴጂ የሰው ልጅ የሚያስፈልጉትን መሠረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት የአጭር ጊዜ የምግብ አቅርቦት ችግርን በማቃለል ዜጎችን በቀጣይ ከከፋ ድህነትና ከተመጣጠነ ምግብ ዕጦት ችግር በራሳቸው ጥረት ደረጃ በደረጃ በማላቀቅ፣ ዘላቂነት ባለው መንገድ እንዲቋቋሙና የተሻለ ኑሮን እንዲመሩ የተመቻቸ ሁኔታ የሚፈጥር ነው፡፡
የምግብ ዋስትና ስትራቴጂው ዝቅተኛ የገቢ ምንጭ ያላቸውንና የመሥራት አቅም ያላቸው ዜጎች ከኅብረተሰቡ ጋር ሆኖ በጥንቃቄ_ በመለየት ጉልበት፣ ሀብት፣ ክህሎትና ዕውቀታቸውን አቀናጅተው ኑሮአቸውን በዘላቂነት ለመምራት የሚያግዙ እሴትን የሚጨምሩ የአካባቢ ልማት ሥራዎችን በስፋት መሥራት ነው፡፡ በቀጣይም ኑሮአችውን ሊመሩበት የሚያስችላቸውን ጥሪት በማፍራት መቆጠብ የሚያስችልና በተደራራቢ የአካል ጉዳት፣ በዕድሜ፣ በጤና፣ ወዘተ ምክንያት በሥራ ላይ መሰማራት ለማይችሉ ዜጎች የቀጥታ ድጋፍ የሚሰጥበትም ነው፡፡ ይህም በመንግሥት፣ በልማት አጋሮችና በኅብረተሰቡ ጥምር ተሳትፎ የሚተገበር ነው፡፡
የምግብ ዋስትና ስትራቴጂ እያንዳንዱ ዜጋ መጠንና ጥራትን ባማከለ መልኩ እንዲሁም ባልተቆራረጠ መንገድ ምግብ ዋስትናው ሊረጋገጥለት እንደሚገባ ያስቀምጣል፡፡ በአንፃሩ ከተሞች ያላቸውንም ዕምቅ ሀብት ባለመጠቀማ ቸውና በአብዛኛው ሊባል በሚችል ደረጃ ከገጠር በሚቀርቡ የግብርና ምርቶች ላይ ጥገኛ በመሆናቸው፣ የምግብ ዋስትና ችግሮችን በመሠረታ ዊነት ማቃለል አልቻሉም፡፡ በከተሞች በተለያዩ አካላት እየተካሄዱ ያሉ በመንግሥት የሚቀርቡ መሠረታዊ ሸቀጦችና ሌሎች የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ሥራዎችም ለደሃ ተብለው የተቀረፁ ቢሆኑም፣ በአፈጻጸም ረገድ ግን ለታለመለት ማኅበራዊ ሥራ የማይደርሱ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሥራዎቹ ያልተቀናጁና ያልተናበቡ በመሆናቸው፣ የሀብት ብክነትና የጥገኝነት ስሜት ከማስፈናቸውም በላይ፣ ዘላቂ ውጤት ማምጣት ላይ ክፍተት ይስተዋልባቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ ዜጎችንና ልዩ ድጋፍ የሚያስፈል ጋቸው የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ሴተኛ አዳሪዎች እንዲሁም አቅመ ደካሞችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ መንግስት ፕሮጀክት ቀርፆ ወደ ተግባር ከገባ አንድ አመት ሆኖታል፡፡ በዚህ አመት ውስጥ በአዲስ አበባ፣ በሀዋሳ፣ በመቀሌ፣ በአዳማ፣ በድሬዳዋ፣ በጅግጅጋና በደሴ እንዲሁም በሌሎች አራት ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ ዜጎችን በስራ እንዲሰማሩ በማድረግና በቀጥታ ድጋፍ በመስጠት ውጤታማ ስራ ተሰርቷል፡፡
የስራ እንቅስቃሴውን አስመልክቶ የከተማና ቤቶች ልማት ሚኒስቴር ከፋና ብሮድካስቲን ኮርፖሬት ጋር በመተባበር ሰሞኑን ውይይት ተደርጓል፡፡ በውይይቱም በከተሞች ምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ስራው ላይ የነበሩ ውጤቶች፣ ችግሮችና በቀጣይ የሚፈቱበት መንገድ ተነስቷል፡፡ በወቅቱም የፌዴራል የከተሞች የምግብ ዋስትና እና የስራ እድል ፈጠራ ኤጀንሲ ተቀዳሚ ምክትል ዋና ዳሬክተር አቶ ሰለሞን አሰፋ እንደተናገሩት፤ በከተሞች ላይ የሚገኙ ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ ዜጎች ተጠቃሚ ለማድረግ በአስራ አንድ ከተሞች ላይ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ስራ ተጀምሯል፡፡
አቶ ሰለሞን፣ በከተሞቹ ላይ በስራ ታታሪነት መጓደል፣ የልማታዊ መልካም አስተዳደር ችግር፣ የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓት አለመኖር እንዲሁም ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ መንስኤ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ለመርሃ ግብሩ ትግበራ በተመረጡት በአስራ አንዱም ከተሞች ባለፈው ዓመት ስራው እንደተጀመረና በአዳማ፣ በሀዋሳ፣ ጅግጅጋ፣ መቀሌ፣ ደሴ እንዲሁም ድሬዳዋ ውጤታማ ስራ መሰራቱን ያመለክታሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከሚገኙ 116 ወረዳዎች ውስጥ በመጀመሪያው ዙር 55 ወረዳዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ ተይዞ ወደ ስራ ቢገባም በስምንት ወረዳዎች ላይ ውጤታማ ስራ አለመሰራቱን ይገልፃሉ፡፡ ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በአረንጓዴ ልማት፣ በደረቅ ቆሻሻና በአካባቢ ልማት ስራዎች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ ገንዘብ እየተከፈላቸው እንደሚገኝ ይጠቁማሉ፡፡
እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ፤ ምንም እንኳን መርሃ ግብሩ በዚህ መልኩ ጥሩ ውጤት እያመጣ ቢሆንም በስራው ላይ የቀጥታ ተረጂዎች ክፍያ ማነስ፣ ለአካባቢ ልማት የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች በጊዜው አለመሟላት እንዲሁም በሚሰሩ የልማት ስራዎች ላይ የሚመለከታቸው ክፍሎች የቅንጅት ጉድለት ተስተውሏል፡፡ ከዚህ አኳያ በልዩ ድጋፍ ስር የሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ሴተኛ አዳሪዎችና ለምኖ አዳሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ ተይዟል፡፡ ሆኖም ስራው በጥናት የተደገፈ መሆን ስላለበት በተያዘው በጀት አመት መጨረሻ ወደ ተግባር ይገባል፡፡
ከአዲስ አበባ የስራ እድል ፈጠራና የከተሞች የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የመጡት አቶ ዘሩ በለጠ በበኩላቸው፤ በመርሃ ግብሩ በከተማው በተመረጡ ወረዳዎች ላይ 55 ወረዳዎች ላይ ከድህነት በታች የሚገኙ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ስራዎች ቢጀመሩም በስምንት ወረዳዎች ላይ ዝቅተኛ ውጤት መምጣቱን ይናገራሉ፡፡ በተቀሩት 47 ወረዳዎች ላይ ግን ውጤታማ ስራ መሰራቱንም ይጠቅሳሉ፡፡
በተፋሰስና በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስራዎች ላይ በጉለሌ፣ በየካና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች ላይ ለውጥ ያመጣ ስራ መሰራቱን የሚጠቁሙት አቶ ዘሩ፤ በቀጥታ ድጋፍ ለሚደረግላቸው ዜጎችም በወቅቱ ክፍያ እንደሚከናወንላቸውም ያመለክታሉ፡፡ በስራ እንቅስቀሴው ላይ በዋናነት በአካባቢ ልማት ስራ ላይ የተሰማሩ ሴቶች የልጆች ማቆያዎች አለመኖር እንደ ችግር ያነሳሉ፡፡
የሀዋሳ ከተማ የከተሞች የምግብ ዋስትና እና የስራ እድል ፈጠራ ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ መልካሙ ሀይሌ እንደሚሉት፤ በከተማው በአንድ ዓመት ውስጥ ቀጥታ ድጋፍ ለሚደረግላቸው ዜጎች 36 ሚሊዮን ብር እንዲከፈል ተደርጓል፡፡ ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ ለማድረግ ቀሪ ስራዎችን የሚጠይቅ ሲሆን፤ በዚህም በቀጣይ 11 ሺ ዜጎችን በአምስት ቀበሌና በሁለት ክፍለ ከተሞች ተጠቃሚ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡
አቶ መልካሙ፣ በዓመቱ ውስጥ ካጋጠሙ ችግሮች መካከል ተጠቃሚዎቹ የባንክ አካውንታቸው ሲጠፋ በምትኩ የሚሰጣቸው አዲስ ቁጥር በመሆኑ ለማስተናገድ መቸገራቸውን ይጠቁማሉ፡፡ በከተማው ላይ የሚገኙ ጎዳና ተዳዳሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግም ስራዎች ቢጀመሩም ወደ ሌሎች ከተሞች በተደጋጋሚ ያለው ፍልሰት እክል መፍጠሩን ይጠቅሳሉ፡፡
የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ ሂሩት ቢራሶ፤ በከተሞች ላይ የህብረተሰቡን ድህነት ለመቀነስና የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝና በዚህም 450 ሚሊዮን ዶላር በእርዳታና በመንግስት ድጋፍ በጀት ተይዞ ስራዎች መጀመራቸውን ይናገራሉ፡፡ በዚህም አራት ሚሊዮን ሰባት መቶ ሺ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ ተይዞ በአንድ አመት ውስጥ በአካባቢ ስራዎችና በቀጥተኛ ድጋፍ ነዋሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡
በምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ስራው ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች ከጥገኝነትና ከጠባቂነት እንዲወጡ ለማስቻል ቀጣይነት ያለው የስራ ፈጠራ ውስጥ እንዲገቡ ለማድረግ እቅድ መያዙን ይጠቅሳሉ፡፡ በአስራ አንድ ከተሞች የሚገኙ ከድህነት በታች የሚገኙ ዜጎች በአረንጓዴ ልማት፣ በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ እንዲሁም በተፋሰስ ስራዎች ላይ ተሰማርተው ገቢ እያገኙ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

መርድ ክፍሉ 

Published in ኢኮኖሚ

ዚምባብዌ አጠቃላይ ምርጫ ለማካሄድ ሁለት ወራት ይቀሯታል፡፡ ይሄም በአገሪቱ ታሪክ ከቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ውጪ የሚካሄድ የመጀመሪያው ምርጫ ይሆናል፡፡ አሁን ያለው አዲሱ መንግሥት በአገሪቱ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የፖለቲካ መስኮች በተወሰነ መልኩ ለውጥ እያመጣ ይገኛል፡፡ የቀድሞው የአገሪቱ መሪ ሙጋቤ ከሥልጣን ከተነሱ በኋላ ዋና ተጠቃሚ የሆኑት የቀድሞ የመከላከያ ኃይል ኮማንደር፣ የአሁኑ አገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሁም ጡረታ የወጡት ጀነራል ኮንስታንቲኖ ችዊንጋ መሆናቸውን አልጀዚራ በድረገፁ አስነብቧል፡፡
አገሪቱን ለሠላሳ ሰባት ዓመት የህግ የበላይነት በሌለበት፣ የአገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በወደቀበት እንዲሁም ሦስት ሚሊዮን ህዝብ ከድህነት ወለል በታች በመሆን ወደ ደቡብ አፍሪካና እንግሊዚ በተሰደዱበት ሁኔታ ሲመሩ የነበሩት ሮበርት ሙጋቤ ሥልጣናቸውን ሲለቁ ብዙዎች ደስታቸውን አደባባይ በመውጣት ገልጸዋል፡፡
የአሁኑ የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ማናንጋግዋ በአገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች ለውጥ ለማምጣት እንቅስቃሴ እያደረጉ ሲሆን፤ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ አገሪቱ ለማንኛውም የንግድ እንቅስቃሴ ክፍት እንድትሆን አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም በፖለቲካው ዘርፍም ለውጥ በመፍጠር የውጭ ባለሀብቶች የሚገቡበትን መንገድ በማመቻቸት ላይ ናቸው፡፡ በአገሪቱ ላይ የተጣለውን የኢኮኖሚ ማዕቀብ ለማስነሳትም ከአሜሪካ ጋር ውይይት ሊያደርጉ እንደሚችሉ ነው ዘገባው የጠቀሰው፡፡
በአሁን ወቅት በአገሪቱ የሚታየው የፖለቲካ እንቅስቀሴ ሰላማዊ ይመስላል፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ሮበርት ሙጋቤ የሚፎካከሯቸውን ፓርቲዎች የውጭ ተላላኪዎች በሚል በመፈረጅና የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲወድቅ ማድረጋቸውን ዘገባው ይጠቁማል፡፡ ነገር ግን ወታደራዊ ኃይሉ ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ የአገሪቱ ወታደሮችና የቀድሞ ወታደሮች በአገሪቱ እየተካሄደ ያለው የአመራር ሁኔታ መስተካከል እንዳለበት፣ የመሠረተ ልማት እንቅቃሴው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባና በሙጋቤ ብቻ ቁጥጥር የሚደረግበት የአገሪቱ ፖለቲካ መለወጥ እንዳለበት ጥያቄ ማቅረቡ ዘገባው ይጠቁማል፡፡
በአሁን ወቅት ችዊንጋ የአገሪቱን የጦር ኃይል ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን መሰረተ ልማት በተመለከተ ለሚደረጉ ሥራዎች ፓርቲውን ወክለው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ የቀድሞ የአየር ኃይል ማርሻል ፔሬንስ ሽሪ የመሬት፣ የግብርናና የገጠር ልማት ሚኒስትር፣ ሌፍተናንት ጄኔራል ሲቡሶ ሞዮ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ንግድ ሚኒስትር፣ የቀድሞ ብርጋዴል ጄኔራል ጆርጅ ሙታንድዋ ቺውሼ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች ፕሬዚዳንት እንዲሁም ሌፍተናንት ጄኔራል ኢንግልበርት ሩጌጅ የፓርቲው የፖለቲካ ዘርፍ መሪ ሆነው እአአ 2017 ታኅሣሥ ላይ መሾማቸውን ዘገባው ያስታውሳል፡፡
የሙጋቤ አስተዳደር ሥልጣን የሚሰጠው ለታማኝ ካድሬዎች ሲሆን፣ ከእነዚህም በተለይ ሲድኒ ሴክሬማሪ፣ ፕሮፌሰር ጆናታን ማዮ፣ ሳቪዮር ካስኩዋሬ እንዲሁም ላግናቱስ ቾምቦ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የማናንግዋግዋ አስተዳደር ደግሞ ሥልጣን የሰጠው ቀድሞ አገሪቱን በወታደራዊ ዘርፍ ላገለገሉ ሰዎችና ለችዊንጋ ታማኝ አገልጋዮች ነው፡፡ አስተዳደሩም የቀድሞ አስተሳሰብ አራማጆች መሆናቸውን ዘገባው ይጠቁማል፡፡
በዚምባብዌ የሚታየው የፖለቲካ እንቅስቃሴ በጓደኝነት ላይ የተመሰረተ ሲሆን፤ ማናንግዋግዋ ለቀድሞ ተፎካካሪ መሪ ሞርጋን ታስቫንጋሪ ዓላማ ትኩረት ሰጥተዋል፡፡ በአገሪቱ የመጀመሪያው የተፎካካሪ ፓርቲ መሪ የነበሩት ሞርጋን ታስቫንጋሪ እአአ 2018 የካቲት ወር ላይ በካንሰር ህይወታቸው ማለፉን ዘገባው ያስታውሳል፡፡
ማናንግዋግዋ በአሁን ወቅት የፖሊስ ኃይሉን፣ የደህንነት ዘርፉንና የአገሪቱን ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የአገሪቱን የምርጫ ኮሚሽን፣ ሁሉንም አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ፣ የጠበቆች ማህበር፣ የአገሪቱን ሚኒስትሮች እና የፓርላማ ፀሐፊውን በቁጥጥራቸው ስር አድርገዋል፡፡ ይህ ደግሞ የፖለቲካ ሥልጣኑን በስሩ ማድረጉ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ እና በዴሞክራሲ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉት በቂ ኃይል እንደሚሰጠው፤ ሙጋቤ ለሠላሳ ሰባት ዓመት ይዘውት ለነበረው የምርጫና የፖለቲካ እንቅስቃሴም አንድ ዕርምጃ ለማሳደግ እገዛ እንደሚኖረው ዘገባው ያለመክታል፡፡
የዚምባቡዌ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን እና ዚምፕ ጋዜጣ በአገሪቱ ከፍተኛ አድማጭና ተነባቢ ቁጥር ያላቸው መገናኛ ብዙሃን ናቸው፡፡ መገናኛ ብዙሃኑ ለህብረተሰቡ ታማኝ በሆነ መንገድ የሚያገለግሉ ሲሆን፤ በአገሪቱ የሚካሄደውን ምርጫ አስመልክቶ ሰፊ ዘገባ በመሥራት የመንግሥትንና የተቃዋሚውን አቋም እኩል እያንፀባረቁ በተለይ ትችቶችን በሬዲዮና በቴሌቪዥን ለህብረተሰቡ እያስተላለፉ ይገኛሉ፡፡ በአገሪቱ የጋዜጣ ህትመት በሆነው ሄራልድ፣ ክሮኒክል እና ማኒካ ፖስት እንዲሁም በድረገፅ በታገዘ መንገድ በፌስቡክና በዩ ትዩብ መረጃዎች ለህብረተሰቡ እየደረሱ እንደሚገኙ ዘገባው ይጠቅሳል፡፡
በአገሪቱ የፓርቲና የመንግሥት ሥራ እንዲለያይ መደረጉ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እገዛ አድርጓል፡፡ በዚህም የመንግሥት ሥራዎች የፓርቲን ሥራና የምርጫ ቅስቀሳ ሥራዎች ላይ ተሳታፊ አይሆኑም፡፡ ይህ ዕርምጃ የመንግሥት ሥራና የፓርቲ እንቅስቃሴ በተለያየ መንገድ እንዲሄድ በማድረጉ ቀድሞ የነበረው አሠራር እንዲሻሻል አድርጎታል፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ግን አሁንም ችግሮች አልተፈቱም፡፡ ለማሳያነትም የአገሪቱ የግብርና ሚኒስትሩ ሸሪ በህገወጥ መንገድ መሬት በወረራ የያዙ እንዲለቁ በማድረግ የግብርና ምርቶችን በማሳደግ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የችዊንጋ ባለቤት ማርይ 300 ሄክታር መሬት ደምቦሻቫ በሚባል አካባቢ እያስተዳደረች እንደምትገኝ ዘገባው ይጠቅሳል፡፡ በእንግሊዝ የሚገኘው ናሃንዳ ሬዲዮ ጣቢያ እንደዘገበውም ሁለተኛ ደረጃ ቀዳማዊ እመቤቷ ከመንግሥት ካዝና በመውሰድ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለውጭ ጉዞ እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡
ዘገባው ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅትን ምንጭ አድርጎ እንዳስቀመጠው፤ በችዊንጋ የሚመራው ወታደራዊ ኃይል በማንሲላንድ በሚገኘው የዳይመንድና የማዕድን ማውጫ ድርጅት ውስጥ እጃቸው አለበት፡፡ በአገሪቱ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን፣ ምርጫ ቦርድና የደህንነት ተቋማትን በድጋሚ የመለወጥ ሥራውን ምርጫው ከመካሄዱ በፊት እየተፋጠነ ይገኛል፡፡ የወታደራዊ ኃይል በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ለማግኘት በኢንቨስትመንትና በዴሞክራሲ ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ነው፡፡
ያለምንም ክርክር የውጭ አገራት ባለሀብቶች ከሙጋቤ አስተዳደር የበለጠ በአሁኑ መንግሥት በፍጥነት ወደ ሥራ ሊገቡ እንደሚችሉ ዘገባው ጠቁሞ፤ ባለሀብቶቹ ኢንቨስት ከማድረጋቸው በፊት ከአካባቢው ከሚገኙ አገራት የበለጠ የተረጋጋ ኢኮኖሚ ማየት ይፈልጋሉ፡፡ በማንጋግዋና በችዊንጋ የሚመራው መንግሥት በመንግሥታዊ ጉዳዮችና በወታደራዊ ሥራዎች ላይ ልምድ ያለው በመሆኑ የባለሀብቱን ፍላጎት ሊያሟላ ይችላል፡፡
የዛኑ ፓርቲ ምርጫውን የሚያሸንፍ ከሆነ ችዊንጋ እአአ 2023 ላይ በትክክለኛው መንገድ የማንግዋግዋ ተከታይ የአገሪቱ መሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ሙጋቤ ከሥልጣናቸው ከመነሳታቸው በፊት ችዊንጋ ለዛኑ ፓርቲ ‹‹በአገራችን የሚካሄደውን ለውጥ እንዳይደናቀፍ ወታደራዊ ኃይሉ ጥበቃ ያደርጋል›› ማለታቸውን ዘገባው ያስታውሳል፡፡ ከዚህም ንግግራቸው በኋላ ለውጡን ወታደራዊ ኃይሉ እንዲቆጣጠረው በማድረግና ከለውጡ በኋላም ወታደራዊ መኮንኖች ወደ ሥልጣን እንዲመጡ አድርገዋል፡፡
የለውጡ ጠባቂዎች የተባሉት ወታደራዊ ኃይሉ ከዚህ በኋላም ችዊንጋን የሚያገለግሉ ይሆናሉ፡፡ በቀጣይ በሚደረገው ምርጫ የኤምዲሲቲ ፓርቲ መሪ ኔልሰን ጫሚሳ የፕሬዚዳንትነቱን መቀመጫ የሚያሸንፍ ከሆነ ደግሞ እአአ 2002 ላይ ተደርጎ እንደነበረው ወታደራዊ ኃይሉ ጣልቃ ሊገባ እንደሚችል ዘገባው ያመለክታል፡፡ በዚህም የአገሪቱ ኢኮኖሚ ሊያሽቆለቁል እንደሚችል ስጋቶች ከወዲሁ እየወጡ ይገኛሉ፡፡
ለዚህም ይመስላል የምርጫ ኮሚሽኑን፣ መገናኛ ብዙሃኑንና የደህንነት ተቋማትን ወደ ማሻሻሉ የተገባው፡፡ መራጩም ህብረተሰቡ በተደበቀ ዴሞክራሲ መንገድ ምርጫውን እንዲያካሂድ ቅስቀሳዎች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ እንቅስቃሴው ግን በግብፅ አብዱል ፈታህ አልሲሲ እንዳደረጉት በዘመናዊ መልኩ አምባገነን መንግሥት በመመስረት አገሪቱን የማስተዳደር ሁኔታዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ዘገባው ያሳያል፡፡ ይህ ከሆነ ዝምባብዌ የወታደራዊው ጄኔራል በግብፅ የፈጸመውን የፕሬዚዳንትነት መንበር የመቆጣጠር ታሪክ ልትደግም ትችላለች፡፡

መርድ ክፍሉ

Published in ዓለም አቀፍ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ተከስቶ የነበረው ሁከትና ብጥብጥ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ወዳጅ አገራት ጭምር ሳይቀር ስጋት የፈጠረ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ መንግስት በወሰደው ብልህ እርምጃ አሁን አሁን ችግሮቹ እየተቀረፉ ቢሆንም እንዲህ አይነት ችግሮች እንዳይደገሙ ግን መስራት ተገቢ ነው፡፡ በተለይ እንዲህ አይነት ግጭቶች ከመፈጠራቸው በፊት ሰላምን ሊያናጉ የሚችሉ ችግሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል፡፡ እንዲህ አይነት ችግሮች ከተፈጠሩ በኋላ ትተው የሚያልፉት ጥቁር ጠባሳ በዘላቂ ሰላም ላይ ጥቁር ነጥብ ትተው የሚያልፉ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ እኔም ይህንን የቅርብ ጊዜ የሰላም እጦት ችግር እያሰብኩ በመካከሉ 27 ዓመታን ወደ ኋላ በትዝታ ተመለስኩ፡፡ የግንቦት ወር መጀመሪያ አካባቢ አገራችን የነበረችበትን ድባብም በአዕምሮዬ ጓዳ ፈተሽኩ፡፡ በርካታ ነገሮች በአይነ ህሊናዬ ተመላለሱ፤ ከነዚህ ውስጥ በተደጋጋሚ ፊት ለፊት የወጣው በወቅቱ የነበረው የሰላም ጉዳይ ነው፡፡
ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው፡፡ የልማት፣ የሰላማዊ ቤተሰብ፣ የተረጋጋ ማህበረሰብ፣ የነገው ትውልድ ተስፋ ወዘተ፡፡ ሰላም ከሌለ ማንም በሰላም ወጥቶ በሰላም ሊገባ አይችልም፤ ሰላም ከሌለ ልጅን ወልዶ ማሳደግና ለአገር መሰረት የሆነውን ማህበረሰብ መፍጠር አይቻልም፤ ሌላው ቀርቶ ህይወቱ ያለፈን ወዳጅ ዘመድ እንኳን በክብር ለማሳረፍ ሰላም ያስፈልጋል፡፡ የአእምሮ እረፍትም ቢሆን ያለ ሰላም አይገኝም፡፡ ሰላም በሌለበት ሁኔታ አንዲት እናት ትምህርት ቤት ስለሄደው ልጇ ማሰብና መጨነቅ የግድ ነው፡፡ ከዚህም ከፍ ሲል ተረጋግቶ ለመኖር ያለንን ተስፋ ሁሉ ያጨልማል፡፡
ሰላም ዘርፈ ብዙ ጉዳይ ነው፡፡ አንድ አገር ሰላም ከሌላት በኢኮኖሚ ጭምር መዳከሟ አይቀሬ ነው፡፡ ለምሳሌ አገር ከምታገኛቸው ገቢዎች አንዱ ከቱሪስት ፍሰት የሚገኝ ገቢ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እውን ሊሆን የሚችለው በሰላም ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ያለበለዚያ ግን ለጉብኝት ቀርቶ ለስራም ቢሆን ሰላም ወደሌለበት አካባቢ የሚሄድ የውጭ ዜጋ አይኖርም፡፡
ስለ ሰላም ሲነሳ በ1983 ዓ.ም ያጋጠመኝና እስካሁን ድረስ ከአእምሮዬ ጓዳ ያልወጣውን አንድ ገጠመኝ ላውጋችሁ፡፡ እለቱ ማክሰኞ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ማለዳ ነው፡፡ በወቅቱ የምኖረው አዲስ አበባ ከጄኔራል ዊንጌት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ አልፍ ብሎ በሚገኝ አወልያ ትምህርት ቤት አካባቢ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረውን ከፍተኛ ውጥረት ተከትሎ የተለያዩ ተቋማትና የመንግስት መጋዘኖች ለዝርፊያ ተጋልጠው ነበር፡፡ ከነዚህም መካከል በሸጎሌ አካባቢ የሚገኘው የጥይት መጋዘን አንዱ ነው፡፡
ከግንቦት 19 ጀምሮ በርካታ ሰዎች በዚህ የጥይት ማከማቻ ስፍራ በመገኘት የሚጠቅመውንም፣ የማይጠቅመውንም ንብረት ሲዘርፉ ቆዩ፡፡ ግንቦት 20 ቀንም የኢህአዴግ ሰራዊት አዲስ አበባ እየገባ ባለበት ሰዓትም ይኸው ቀጥሎ ነበር፡፡ በግምት አራት ሰዓት አካባቢ ግን አካባቢውን ያስደነገጠ ከባድ ፍንዳታ ተከሰተ፡፡ በዚህ ጊዜ ከሸጎሌ የወጣው ፍንዳታ ከአካባቢው አልፎ እስከ አንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ ቤቶችን ጭምር ለጉዳት የዳረገ ነበር፡፡ በእለቱ በአካባቢው ላለው እና ይህንን ትዕይንት ለተመለከተ ሁሉ የአዕምሮ እረፍትን የሚነሳ ክስተት ነበር፡፡ በዚህ ፍንዳታ ከአንድ ቤተሰብ እስከ አምስት ሰው ህይወት ያለፈበት ዘግናኝ ክስተት ተፈጥሮ አልፏል፡፡ በዚያው ሰሞን በበቅሎ ቤት አካባቢ በተከሰተው የነዳጅ ዴፖ ፍንዳታም በሌሊት ቤት ንብረታቸውን ጥለው ከከተማዋ የወጡ በርካታ ዜጎች ነበሩ፡፡
እነዚህ ሁሉ ክስተቶች ሰላም ከመጥፋቱ ወይም በወቅቱ ከነበረው የሰላም መደፍረስ ችግር የመነጩ ናቸው፡፡ ያም ሆኖ ግን ግንቦት 20 እነዚህን ክስተቶች በመቀነስ ረገድ ያበረከተው አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም፡፡ በታሪክ በጉልህ ከሚፃፉ የግንቦት 20 ገፀ በረከቶችም ውስጥ ሰላም አንዱ ነው፡፡
ለ17 ዓመታት ኢትዮጵያን ባልተረጋጋ ሁኔታ የመራው የደርግ መንግስት በተለይ በመጨረሻ ዘመኑ ላይ ተስፋ የቆረጠበት ዘመን እንደነበር ይታወቃል፡፡ ለዚህም አንዱ ማሳያ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው ላይ አንስቶ ለጦርነት ወደ ማሰልጠኛ እስከማስገባት መድረሱ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ወደ ጦር ሜዳ በመላክ በጦርነት ድል አደርጋለሁ ብሎ ማሰብ ምን ያህል ድክመት እንደሆነ መገንዘብ አያዳግትም፡፡
በአንዳንድ አገራት ተማሪዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ወደ ውትድርና ማሰልጠኛ ጣቢያ ገብተው ስልጠና የሚወስዱበት ሁኔታ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ይህ ግን ተማሪዎቹን በቀጥታ ወደ ጦርነት ለማሰማራት ሳይሆን አካላዊና አዕምሮአዊ ዝግጁነትን ለመፍጠር ነው፡፡ ከዚህ በዘለለ ግን ብዕርና ወረቀትን ብቻ ሲያዋድድ ለኖረ ወጣት በአንድ ጊዜ ተነስና ዝመት፣ ተዋግተህ ሙት ማለት አንድም ልጆቹን ለአደጋ ማጋለጥ፣ አልያም ማህበረሰቡን ተስፋ ከማስቆረጥ የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም፡፡
በዚህ አይነት ሁኔታ በትልቅ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ የነበረው የደርግ መንግስት አገርን ለመጠበቅ የሚያስችል ቁመናና ብቃት ላይ ያልነበረበት ወቅት ነበር፡፡ በአጠቃላይ በወቅቱ በዚህ የግንቦት ወር መጀመርያ ላይ የነበረው ሁኔታ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የጭንቀት ወቅት ነበር፡፡ ይባስ ብሎ ለ17 ዓመታት ኢትዮጵያን ሲመሩ የነበሩት ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም አገሪቷ በዚህ ሂደት ላይ እንዳለች ጥለው መኮብለላቸው ህዝቡን ለጭንቀትና ለስጋት የዳረገበት ወቅት ነው፡፡
በዚህ ወቅት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እንደየዕምነቱ በአገራችን ሰላም እንዲፈጠር የሚፀልይበት ወቅት ነበር፡፡ በተለይ አዲስ አበባ የነበረው ሁኔታ የተለየ ነበር፡፡ ከተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የያዘውን ታንክና ከባድ መሳሪያ አንግቦ ወደ አዲስ አበባ ይተም የነበረው ሰራዊት አዲስ አበባ ከገባ በኋላ ምን ይፈጠራል በሚል ስጋት እናት ልጇን የምታስገባበት ቦታ እስከሚጠፋት ድረስ ጭንቀት የሰፈነበት ጊዜ ነበር፡፡
ያም ሆኖ ግን ከዚህ ሁሉ የጭንቀት ጊዜ በኋላ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ነገሮች ተለወጡ፡፡ አዲስ አበባ የጦርነት ቀጣና ትሆናች ሲሉ የነበሩ ሁሉ ህልማቸው እውን ሳይሆን ቀርቶ በከተማዋ መረጋጋትና ሰላም ሰፈነ፡፡ ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት የነበረውን የአገራችንን የሚዲያ መረጃ የሚከታል ሁሉ የእያንዳንዷ ቀን የውሎ መረጃ ዜና ከጦርነት ጋር የተያያዘ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ በሌላም በኩል 15 ዓመት የተጠጋው ወጣት ሁሉ ለእናቱ የስጋት ምንጭ የሆነበት ዘመን ነበር፡፡ ምክንያቱም በዘመኑ ወጣቶችን በአፈሳ ከየቤቱ እየለቀሙ ወደ ጦርነት ማጋዝ የተለመደ ስለነበር እናቶች ያለእረፍት ለመኖር የተገደዱበት ጊዜ ነው፡፡ የደረሰ ልጇን በቁም ሳጥን ውስጥ ደብቃ መቆለፍ ፣ በዱቁት እቃ ውስጥ ማሸግ፣ በጣሪያ ስር ኮርኒስ ላይ መደበቅ፣ ወዘተ የዘመኑ ትውስታዎች ናቸው፡፡
በዚህ አጋጣሚም በአንድ ወቅት የደረሰብኝን በጥቂቱ ላካፍላችሁ፡፡ ወቅቱ የብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት የተጀመረበት ዘመን ነው፡፡ በቤታችን ውስጥ ከእናትና አባታችን በተጨማሪ ታላቅ እህቴና ታላቅ ወንድሜ አብረን እንኖራለን፡፡ ታላቅ ወንድሜ ገና አፍላ ወጣት በመሆኑ እናቴ ሁል ጊዜ እንቅልፍ አልነበራትም፡፡ ከዛሬ ነገ ይወስዱብኛል በሚል ስጋት ያለእንቅልፍ ማሳለፍ የዘወትር ስጋቷ ነበር፡፡ እንደፈራችውም አንድ ቀን ወንድሜ ከትምህርት ቤት ሲመለስ ከመንገድ ላይ ተይዞ ወደ ውትድርና ተወሰደ፡፡ ይህ ወቅት በቤታችን ውስጥ ትልቅ የሃዘን ስሜት የፈጠረ ነበር፡፡ በተለይ ለእናቴ ከዚህ በላይ ህመምና በሽታ አልነበረም፡፡ ይህ ወቅት እስከዛሬ ድረስ በውስጤ ይመላለሳል፡፡ አንድ ሰው ሳይፈልግ ወደ ጦርነት የሚወሰድበትና የሚሞትበት አገር፤ ያውም ባላመነበት ጦርነት፡፡
ይህ ዘመን እነሆ ታሪክ ሀኖ ካለፈ 27 አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት ካፈራናቸው ሀብቶቻችንም ውስጥ አንዱና ዋነኛው ሰላም ነው፡፡ በነዚህ ዓመታት ቢያንስ ተገዶ ወደ ጦርነት መጓዝ የለም፡፡ በየቀኑ ስለጦርነት የምንሰማበት ጊዜም አብቅቶ ስለልማትና ስለሰላም መስማት ተለምዷል፡፡ እንደቀይ ሽብር አይነት በአደባባይ የሚደረግ ርሸናና ለሞተው ልጅ አስከሬን ለመውሰድ ገንዘብ አምጡ መባልም የለም፡፡
ስለ ሰላም ለማውራት የግድ ጦርነት ውስጥ ገብተን ማየት አለብን የሚል የዋህ አስተሳሰብ ሊኖረን አይገባም፡፡ ብልህ ሰው ችግሮችን ከሌሎች ችግር ይማራል፡፡ ችግሩን ካላየሁ አላምንም የሚል ካለ ግን የዋህ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን አሁንም ቢሆን ስላለፈው ሁኔታ ያልተረዱ አንዳንድ ወጣቶች ሰላምችንን ሊያሳጣን ወደሚችል ድርጊት ውስጥ ሲዘፈቁ ይታያል፡፡ ከዚህ አንፃር በአንድ ወቅት ያጋጠመኝም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ቦታው አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት፡፡ በእለቱ በዚህ አካባቢ ይከበር በነበረው የደመራ በአል ላይ ለመሳተፍ በርካታ የከተማችን ነዋሪዎች የተገኙበት እለት ነበር፡፡ በተለይ በርካታ የከተማችን ወጣቶች በስፍራው ታድመዋል፡፡
በዚህ መካከል ጥቂት ወጣቶች በመንግስት ላይ ተቃውሞ ማሰማት ጀመሩ፡፡ ጠጋ ብዬ ወጣቶቹ የሚሉትን ለመስማት ጥረት አደረኩ፡፡ የወጣቶቹ ድምፅ “መንጌ ናፈቀኝ” የሚል ነበር፡፡ የወጣቶቹን እድሜ ስገምት አብዛኞቹ በአስራዎቹ መጨረሻ ወይም በሃያዎቹ መጀመርያ ላይ መሆናቸውን ለመገመት አላዳገተኝም፡፡ እነዚህ ወጣቶች ደግሞ በዚህ ሥርዓት ውስጥ የተወለዱ ናቸው፡፡ ቀደም ሲል የነበረውን ሥርዓት የማያውቁ ብቻ ሳይሆን በቅጡ ያልተረዱ መሆናቸውንም ተረዳሁ፡፡ እናም የማያውቁትን መናፈቃቸው ገርሞኝ ወደ ቤቴ ተመለስኩ፡፡
ይህ የወጣቶቹ ድርጊት ለረጅም ጊዜ በአእምሮዬ ሲመላለስ ነበር፡፡ እውን እነዚህ ወጣቶች ምን እያሉ እንደሆነ በትክክል ያውቁታል? ስለሚናገሩት ሥርዓትስ በቅጡ ያውቃሉ? የሚሉ ሃሳቦች የአዕምሮዬን ጓዳ አጨናነቁት፡፡ በዚህ መካከልም በርካታ ሃሳቦችን ማውጣትና ማውረድ ጀመርኩ፡፡ ለዚህስ ተጠያቂው ማነው? የሚለው ጉዳይም ይበልጥ እንዳስብበት ገፋፋኝ፡፡
አገራችን በደርግ ዘመን ከነበረችበት የጭቆና ዘመን ተላቃ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመርን መከተሏ ይታወቃል፡፡ የአገራችንን ነባራዊ እውነታ ስንመለከት ደግሞ አብዛኛው ህዝባችን ወጣት ነው፡፡ ይህም አብዛኛው ህዝባችን የዚህ ሥርዓት አካል እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ህዝብ ደግሞ የቀደመውን ሥርዓት ምንነትና ባህርይ በአግባቡ እንዲያውቅና እየተጓዘበት ያለውን መስመር በአግባቡ ተረድቶ ከመንግስት ጎን እዲቆም ማድረግ ከመንግስት ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን ይህንን በአግባቡ ካላስገነዘብንና ካላሳወቅን አፈንጋጭ ትውልድ መፈጠሩ አይቀርም፡፡
ከቅርብ ዓመታ ወዲህ በአገራችን የታየውም ሁኔታ ከዚህ የመነጨ ይመስለኛል፡፡ በተለይ ስለቀደመው ሥርዓቶች ታሪክን ከማስተማርና እየተሰራበት ያለውንም በአግባቡ እንዲያውቅ ከማድረግ አንጻር ክፍተቶች አሉ፡፡ አሁን ላይ ስለሀገሩ የሚያውቅ ትውልድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ እንደመጣ ብዙዎች ሲናገሩም መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡
በአጠቃላይ በአስተሳሰብ ቀረጻ ላይ እየሰጠን ያለነው ትምህርት አነስተኛ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ቀደም ሲል በነበሩ ሥርዓቶች ውስጥ ያለፉ ወላጆችም አሁን ላይ ላሉ ወጣቶች ስለነበረው ነባራዊ ሁኔታ ትክክለኛውን ነገር ከማሳወቅ አንፃር ትልቅ ክፍተት አለባቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ልጆቻቸውን በኮርኒስ ውስጥ እስከመደበቅ የደረሱና እራሳቸውም በዚሁ ሁኔታ ያለፉ ዜጎች ይህንን ነባራዊ ሁኔታ ለመጪው ትውልድ በግልፅ አለማሳወቅ እውነታን እንደመካድ ይቆጠራል፡፡
እስኪ በቅድሚያ እድሜያችን ከ30 ዓመት በላይ የሆነን ዜጎች አንድ የጋራ የቤት ስራ ወስደን እንሞክር፡፡ በርግጥ ከ30 ዓመት በላይ ስል ሁሉም ያንን ሥርዓት በትክክል ያውቀዋል ለማለት እንዳልሆነ ልብ በሉ፡፡ አንዳንዶቻችን በጭላንጭልም ቢሆን ከወላጆቻችን ሁኔታ ውን ተረድተን ይሆናል ከሚል ግምት የተወሰደ ነው፡፡ እናም በወቅቱ በየቤታችን የነበረውን ጭንቀትና ነገ ምን ይሆን እያልን እናሰላስል፡፡ አንድ የቀበሌ ሊቀመንበር በቀላሉ ህይወታችንን ሊቀጥፍ የሚችልበት ነባራዊ ሁኔታ አልነበረም? በዘመኑ የነበረው ወጣትስ የሚፈልገውን ሃሳብ ሰብሰብ ብሎ ለመነጋገር ነፃነት ይሰማው ነበር? እነዚህን ሃሳቦች ለራሳችን አእምሮ ትተን ወደ ዛሬ እንመለስ፡፡
በርግጥ ዛሬም ቢሆን በአገራችን በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች ግን ከሰላም ይልቅ የመልካም አስተዳደርና የኢኮኖሚ ችግሮች ናቸው፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ደግሞ የጥረት ሜዳው ተዘርግቷል፡፡ በዚህ ሜዳ ሰርቶ ለመለወጥ የተሻለ ጊዜ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን አገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ የህዝብ ቅሬታዎች ማስተናገድና እዚህም እዚያም ግጭቶችን መስማት የተጀመረበት ሁኔታ እናገኛለን፡፡ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገራችን እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችና የሰላም እጦት ችግሮች እየተባባሱ መጥተው መንግስት ከአንድም ሁለት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጅ አስገድዶታል፡፡
ያም ሆኖ ግን ባለፉት 27 ዓመታት አገራችን ሰላማዊ ምድር በመሆኗ ያገኘናቸው በርካታ ድሎች አሉ፡፡ በነዚህ ዓመታት የህዝብን በሰላም ወጥቶ በሰላም የመግባት ነፃነት ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጦርነት የኢኮኖሚ ድቀት ጠንቅ በመሆኑ ይህንን ለጦርነት ይውል የነበረ ሀብት ሀገርን ለማሳደግ ተጠቅመንበታል፡፡ አገራችን አሁን ከደረሰችበት ደረጃ የደረሰችው ላለፉት ዓመታት ሰላም በመኖሩ ብቻ ነው፡፡ ይህ ሰላም ባይፈጠር አሁን ላይ ከህዝብ ቁጥሩ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መሄድ ጋር ተደምሮ አስከፊ ሁኔታ ይፈጠር እንደነበር መገመት አያዳግትም፡፡
ከሁሉም በላይ ግንቦት ሃያ ይህንን የሰላም በረከት ይዞልን መምጣቱ አንድ ትልቅ ውጤት ነው፡፡ ይህንን የሰላም በረከት ደግሞ መጠበቅ የኛ ፈንታ ነው፡፡ ይህ እድል ከእጃችን ካመለጠ ነገ ልንመልሰው አንችልም፡፡ የሰላም አስከፊው ገፅታው አንዴ ከእጅ ካመለጠ ለመመለስ አስቸጋሪ መሆኑ ነው፡፡ ይህንን ደግሞ ከነ ሶማሊያ ሶርያ፣ የመን፣ ኢራቅ፣ ሊቢያ እና ሌሎች አገራት ተሞክሮ በቅርበት አይተናል፡፡ እነዚህ አገራት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች አገራት የሚተርፉ እንዳልነበሩ ዛሬ ላይ ግን የሰላም እጦት በአንድ ጊዜ ቁልቁል እንዲወርዱና የድህነትን ወለል እንዲረግጡ አድርጓቸዋል፡፡ እናም “ሞኝ ከራሱ፣ ብልህ ከሌላው ይማራል” እንደሚባለው ሰላማችንን አጥብቀን እንያዛት፡፡

ውቤ ከልደታ

Published in አጀንዳ

ኢትዮጵያ ከሶስት ሺ ዓመት በላይ ታሪክ ያላት ቀደምት የስልጣኔ መሰረት መሆኗ ይታወቃል፡፡ በዚህ የኋላ ዘመን ታሪኳ በአንድ ወቅት የከፍታ ዘመን ላይ የነበረች ቢሆንም ብዙህነት ማስተናገድ አቅቷት ወደኋላ ተመልሳ የድህነትና የጦርነት ተምሳሌት ሆና ቆይታለች፡፡ ብዙህነት ባልተስተናገደበት በፊውዳላዊው ዘውዳዊ ሥርዓተ መንግስትም ሆነ በዘመነ ደርግ ኢትዮጵያውያን ሀገራዊ አንድነታቸውን ጠብቀው ኖረዋል፡፡
በየዘመኑ የነበረው የኢትዮጵያውያ አስተዳደር የዜጎችን መብት የማያከብርና ኢ-ዴሞክራሲዊ መሆኑ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የዘመናዊ ስልጣኔ እያደገ መምጣት ዜጎች ስለመብታቸው ይበልጥ እንዲያውቁና እንዲታገሉ አድርጓቸዋል፡፡ አገራችንም የበርካታ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አገር እንደመሆኗ እያንዳንዱ ብሄር፣ ብሄረሰብም የራሱን መብት መጠየቅ ጀመረ፡፡ በተለይ በየቦታው የነበሩ ገዢዎች ለራሳቸው ጥቅም ህዝቡን የሚጨቁኑበት አገዛዝና ግፍ እየበዛ በመሄዱ የመብት ጥያቄዎችም በዚያው ልክ እያደጉ የመጡበት ሁኔታ እንደተፈጠረ የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ፡፡
ከዚህ በኋላም ቀስ በቀስም የብሄሮች፣ ብሄሰረቦችና ህዝቦች ጥያቄ ወደ የተደራጀ ሃይል ተለወጠ፡፡ ትግሉም ዘውዳዊውን አገዛዝ በመጣል ደርግ ስልጣን ላይ እንዲወጣ ምክንያት ሆነ፡፡ ያም ሆኖ ግን ደርግ ወደ ስልጣን የወጣበት መንገድ በራሱ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦች መብት ለማስጠበቅ ሳይሆን በአቋራጭ ስልጣን የያዘ አካል በመሆኑ በዘመኑ የነበረውን የመብት ጥያቄ ሊመልስ የሚያስችል ቁመና አልነበረውም፡፡ በተለይ በዘመኑ ተከስቶ የነበረው የተማሪዎች ጥያቄ የብሄር ብሄሰቦች መብት እንዲከበር የሚጠይቅ በመሆኑ የደርግ መንግስት ይህንን ከመመለስ ይልቅ በሃይል ለመጨፍለቅ ሙከራ ያደረገበትና መልሶ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት ማፈን የጀመረበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡
ሆኖም በኢህአዴግ በተመራውና የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለ17 ዓመታት ያካሄዱት መራር ትግል የደርግ ሥርዓት ሊወድቅ ችሏል፡፡ በሂደትም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበትንና ብዙህነትን የሚያከብር አዲስ ህገመንግስት በትግላቸው እውን አድርገዋል፡፡
አዲሲቷ ኢትዮጵያ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብቶች የተከበሩባት ብቻ ሳትሆን አንድነታቸው በፍላጎት ላይ ተመስርቶ እውን የሆነበት፣ እያንዳንዱ ብሄር ብሄረሰብም መብቱ ተከብሮለት ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር እድሉን ያገኘበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ የተነሳም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የብሄር ብሄሰቦችን መብት እስከመገንጠል ድረስ ያጎናፀፈ ነው፡፡
ይህ መብት ግን የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄሰረቦችና ህዝቦች ከአንድነት ይልቅ መከፋፈልን፣ ከመተባበር ይልቅ መጎነታተልን እንዳያስከትል ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ በህገመንግስታችን በግልፅ እንደተቀመጠው በአገራችን የሚገኙ ሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩል ህገመንግስታዊ መብት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይህ መብት እውን የሚሆነው ደግሞ አንዱ የሌላውን መብት በማክበርና ርስ በርስ በመከካበር፣ እንዲሁም በመተባበር በጋራ ተያይዞ ማደግ ላይ ሲመሰረት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት እንዲያብብና እንዲጎለብትም መስራት ተገቢ ነው፡፡
አልፎ አልፎ ከዚህ ህገመንግስት ባፈነገጠ መልኩ የኢትዮጵያን አንድነት የማይፈልጉ ሃይሎች የመንግስትን አወቃቀርና የብሄር ብሄረሰቦችን መብት ለተሳሳተ ዓላማ ሲጠቀሙበት ይስተዋላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት አስተሳሰብን በሚጻረር መልኩ እያንዳንዱ ኢትዮጵዊ ዜጋ በአገሩ ውስጥ ከአንድ ክልል ወደ ሌላው ክልል ተዘዋውሮ የመስራት እና የመኖር መብቱን ሊገድቡ የሚችሉ ችግሮችና እንቅፋቶች ሲፈጠሩ ታይተዋል፡፡ በብሄር ብሄረሰቦች መካከልም ለዘመናት የቆየውን አብሮ የመኖርና የመቻቻል ባህል የሚሸረሽሩ ግጭቶች ሲፈፀሙ ቆይተዋል፡፡ እነዚህ ችግሮች ግን ከአንድነት ይልቅ መበታተንን፣ ከእድገት ይልቅ ኋላቀርነትን የሚያስከትሉ በመሆኑ አጥብቀን ልንታገላቸው ይገባል፡፡
ከዚህ ቀደም ያገኘናቸው ድሎችም ሆኑ የታገልንለት አላማ ለመበታተን ሳይሆን አንዲት ጠንካራ እና ለህዝቦቿ የተመቸች ሉኣላዊ አገር ለመገንባት መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት አይገባም፡፡ ግንቦት 20 ካስገኘልን በርካታ ድሎች ውስጥም አንዱ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ነፃነት ነው፡፡ ይህ ነፃነት ደግሞ ዘላቂ የሚሆነው በዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት አስተሳሰብ እያንዳንዳችን የራሳችን መብቶች በማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብቶችም ማክበርና ማስከበር ስንችል በመሆኑ ርስ በርስ ያለንን የአብሮነትና የአንድነት መንፈስ አጥብቀን መያዝ ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡ አንድነታችንም በማይፈርስ መሰረት ላይ ይገነባል፡፡ይጠናክራል፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

በኢትዮጵያ ከአገራዊ አንድነት ይልቅ ጠባብ ብሔርተኝነት እየገነነ መምጣቱ ይነገራል፡፡ በመሆኑም ህብረ ብሔራዊ አንድነትን የገነባች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ብሔርተኝነትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ማስተዳደር እንደሚገባ ምሁራን ይገልፃሉ፡፡

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካ ሳይንስና ስትራቴጂ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር መረሣ ፀሐዬ እንደሚናገሩት፤ በአገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ትልቁ ጉዳይ ብሔር የሚበየንበት መንገድ ነው፡፡ ለምሳሌ በምዕራቡ ዓለም ግለሰብ ላይ የተመሰረተ እኩልነት፣ ነጻነትና አንድነት በሚል ሲሆን፤ በሦስተኛው ዓለምና እንደሩሲያ ያሉት ደግሞ የጋራ ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋና መልክዓ ምድር ያላቸው መሆኑን መሰረት በማድረግ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን ብዝሃነትን የተቀበለና ያከበረ የኢትዮጵያዊነት ግንባታ አማራጭ የሌለው ነው፡፡ በታሪክ አጋጣሚም አሁን ያለችውና ብዝሃነት ጎልቶ የሚታይባት ኢትዮጵያ ተፈጥራለች፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር የሆኑት ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ በበኩላቸው፣ እንደሚናገሩት፤ ኢህአዴግ ሲመጣ በመጀመሪያ የወሰደው እርምጃ የብሔር እኩልነትን ማረጋገጥ፤ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ ርቀት ሄዷል፡፡ ሆኖም አካሄዱ መልኩን በመሳቱ ክልሎች በአንድ አገር የሚኖሩ አልመስል ብለዋል፡፡ ክልሎች ራሳቸውን እንደ አገር የሚተያዩበት፣ እንደ ሁለት አገርም መሬትና ህዝብ የሚቀራመቱበት ሂደትም ተፈጥሯል፡፡
ይህ የተሳሳተ ብሔርተኝነት ነው፤ አካሄዱም ዴሞክራሲያዊ አይደለም፡፡ በተመሳሳይ የህዝቦች አመለካከትን ጨምሮ በጥበት፣ ትምክህት፣ የቀድሞ ስርዓት ናፋቂና ሌላም በማለት በተለያየ መልኩ እየፈረጁ መሄድ በምንም መልኩ ዴሞክራሲያዊ ባህሪና መገለጫ የሌለው ብሔርተኝነት ነው፡፡ አካሄዱም በህዝቦች መካከል ከአንድነት ይልቅ መለያየትና መራራቅን ይፈጥራል፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ኢትዮጵያዊነትን ለማጠናከር ብሔርተኝነቱ ዴሞክራሲያዊ ሊሆን፤ አንዱ ብሔር የሌላውን ማንነት ሊያከብርና እውቅና ሊሰጥ ያስፈልገዋል፡፡ የብሔር ማንነት እያደገና እየጠነከረ መሄዱ ተፈጥሯዊ ቢሆንም፤ ብሔርተኝነቱ ግን ዴሞክራሲያዊ ከሆነ፤ ብሔር ብሔረሰቦች በወንድማማችነት እየተያዩ ለመኖር፣ ቀደም ሲል የነበሩ የተዛቡ ግንኙነቶችን ለማረምና አንድነትንም ለመጠበቅ ያስችላል፡፡

በዚህ ሃሳብ የሚስማሙት ረዳት ፕሮፌሰር መረሣ በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ በኢትዮጵያ ችግር የሚሆነው የብሔርተኝነት መኖር ሳይሆን፤ ይሄንን የማስተዳደሩ ሂደት ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም የማንነት አስተዳደር ሂደቱ አንድም ጽንፍ የወጣ ብሔርተኝነት እንዲፈጠር የሚያደርግ ሲሆን፤ በሌላ በኩል የጋራ ባህልና ታሪክን በአንድ ላይ በማምጣት፣ በሂደት እየተቀበሉ፣ በኢኮኖሚ ሽግግርም እያጠናከሩ በመሄድ አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚያግዝ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያዊነት ባለው ብዝሃነት መለካት፤ ብዝሃነትን የተቀበለ ብሔርተኝነትንም በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚተዳደርበት ሂደት መፈጠር ይኖርበታል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር መረሣ እንደሚሉት፤ አሁን ላይ የተገነባው ብሔራዊ ማንነት በየቦታው ተበታትኖ ያለ፤ ወደ ማዕከል መምጣት ያልቻለ ነው፡፡ ሆኖም ብሔርተኝነትን በዴሞክራሲያዊ መልኩ ማስተዳደር ሲቻል ይህ ተበታትኖ ያለ ማንነት በኢኮኖሚ ትስስርም ሆነ በጋራ እሴት ግንባታዎች ወደ ማዕከል በማሰባሰብ የጋራ ማንነትን ለመፍጠር ያግዛል፡፡ ህዝቦች ያገኙትን የህግና የፖለቲካ እውቅና ወደ ልማትና ማህበራዊ ፍትህ ለማምጣትም ያስችላል፡፡ ብሔርተኝነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ኢትዮጵያዊነትም ታላቅ መሆኑን ለመገንዘብ ዕድል ይፈጥራል፡፡
ኢትዮጵያም የመጨረሻ ቅርጿን የያዘችው በአፄ ምኒልክ ዘመን ሲሆን፤ ከዚያ በኋላ የነበረው ኢትዮጵያዊነትን የመፍጠር ሥራ ስለነበር የተለያየ ቋንቋና አስተዳደር ያላቸው ሰዎች ወደ አንድ የመጡበት መሆኑን ነው ረዳት ፕሮፌሰር መረሣ የሚናገሩት፡፡ በዚህ ሂደት ግን የታዩ ሁለት እውነታዎች አሉ፡፡ አንዱ እስከ 1960ዎቹ የተማሪዎች አመፅ ድረስ የነበረው ኢትዮጵያዊነት በአንድ ሃይማኖት፣ ቋንቋና ማንነት እንዲገለጽ የተደረገበት ሲሆን፤ ዘመናትን ቢዘልቅም ብዝሃነትን ያላከበረና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የማይወክል በመሆኑ ተቀባይነት ሳያገኝ ተቀልብሷል፡፡ ይሄም ብዝሃነትን የተቀበለ ኢትዮጵያዊነትን ወደመገንባት እንዲኬድም ምክንያት ሆኗል፡፡
እንደ ዶክተር ሲሳይ ማብራሪያ፤ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እንዲያብብና ከሁሉም በላይ ደግሞ ለጋራ አገር ግንባታ ሂደት አስተዋጽዖ እንዲኖረው ካስፈለገ እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ ለራሱ የሚሰጠውን ትርጉምና ግምት ያክል ለሌላውም ማሳየት አለበት፡፡ አሁን የማህበራዊ ሚዲያውን ጨምሮ የሚታዩ ጥቂት ግለሰቦች ከአንዱ ብሔር ተገን በመያዝ ሌላው ብሔር ላይ ስድብና ማጥላላት የመሰንዘር አዝማሚያዎች በጊዜ ሀይ ካልተባሉ ወደህዝቡ ሊወርዱና ህዝቡም ስሜቱን ሊጋራ የማይችልበት፣ ቁርሾም የማይፈጥርበት ዕድል አይኖርም፡፡ ኢትዮጵያም ሌሎች አገራት ላይ የደረሰው ችግር አይደርስባትም፣ ወደቀውስና መበታተን አትሄድም ማለት አይቻልም፡፡
በዶክተር ሲሳይ ሃሳብ የሚስማሙት ረዳት ፕሮፌሰር መረሣ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ አሁንም ብሔርተኝነትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ማስተዳደር ካልተቻለ፣ የህዝብ ጥያቄዎች ይበረክታሉ፤ መንግሥትም እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ይከብደዋል፡፡ ይህ ሲሆን ዜጎች በብሔር ማንነታቸው ይደበቃሉ፤ ጽንፍ የወጡ የብሄርተኝነት አስተሳሰቦች ይወለዳሉ፤ የመገንጠል ጥያቄዎች ይነሳሉ፤ አገርን የመበተን አዝማሚያዎችም ይመጣሉ፡፡

ዜና ትንታኔ

ወንድወሰን ሽመልስ

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።