Items filtered by date: Wednesday, 16 May 2018

በብስክሌት ስፖርት ኢትዮጵያ በዓለም የውድድር መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ ብቅ ያለችው በአውስትራሊያዋ ሜልቦርን ከተማ እኤአ በ1956 በተካሄደው 17ኛው ኦሎምፒያድ ነው። በወቅቱ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን በመወከል አስራ ሁለት ብስክሌተኞች (ተወዳዳሪዎች) ተሳታፊ ሆነዋል። ከዚህ የጀመረው የኢትዮጵያና የብስክሌት ስፖርት ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ዓመታትን ተሻግሯል። ስፖርቱ አሁን ካለበት ደረጃ ሲደርስ አንድ ጊዜ ከፍ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዝቅ በማለት ተጉዟል።
ከውጤት ርቆ ጠፋ ሲባል፤ የታሪክ ክስተት የሚመስሉ ብስክሌተኞች ባልታሰበ አጋጣሚ ብቅ በማለት በዓለም የውድድር መድረክ ውጤት ሲያስመዘግቡ ስፖርቱም መኖሩ ይታወሳል፡፡ እነዚህ ብስክሌተኞች ስፖርቱ እንዳይረሳ በማድረግ ከዛሬ ደጃፍ አድርሰውታል፡፡ በኢትዮጵያ የብስክሌት ስፖርት የተለያዩ ሂደቶችን አልፏል፡፡ የዕድገትና የውድቀት ምዕራፎችን ገልጿል።
በዚህ የታሪክ ሂደት የአዲስ አበባ የብስክሌት ስፖርት ፌዴሬሽን አብሮ ተጉዟል፡፡ ፌዴሬሽኑ በአገሪቱ የብስክሌት ስፖርቱ ዕድገትና ውድቀት ተካፍሏል፡፡ በመዲናይቱ የብስክሌት ስፖርት ከፍታ በሚዘመርበት ወቅት፤ በቁጥር የበረከቱ ክለቦችን በማቀፍ ለስፖርቱ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽዖ አበርክቷል። እነ ገረመው ደንቦባን የመሳሰሉ ስፖርተኞችን ማፍራት ችሏል፡፡ የብስክሌት ስፖርት ውድቀት በሚባልበት ጊዜ ደግሞ ክለቦችን አፈራርሶ በመቀመጥ ተወቃሽ ሆኗል።
በእነዚህ ሁለት የታሪክ ጽንፎች የሚጠቀሰው የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን አሁን ላይ ተስፋ ሰጭ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑ ይነገራል፡፡ በተለይም የክለብ ጥንካሬውን መልሶ ለመጨበጥ ጅምር ሥራዎችና ለውጦች ማሳየቱ ነው የሚጠቀሰው፡፡ የፌዴሬሽኑን ወቅታዊ እንቅስቃሴዎች፣ ያለፈውን ስኬት፣ ተግዳሮቶችና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስፖርት ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚ እና የከተማዋ የብስክሌት ስፖርት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ረዘነ በየነ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፦ የአዲስ አበባ የብስክሌት ስፖርት ፌዴሬሽን ከአገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ ያስቻለ አቅም እንደነበረው ይነገራል፡፡ ይሄን ቢያብራሩልን?
አቶ ረዘነ፦ የብስክሌት ስፖርት በአዲስ አበባ ከተማ ተጽዕኖ እንደነበረው የሚነገረው እውነት ነው። ከዛሬ 30 እና 40 ዓመታት በፊት ከእግር ኳስ እና ሌሎች ስፖርቶች በተለየ መልኩ የብስክሌት ውድድር በህብረተሰቡ ዘንድ ተወዳጅነት ነበረው። የስፖርት ቤተሰቡ በውድድር ቦታዎች ላይ በመገኘት ለዘርፉ የነበረውን ፍቅር ያሳይ ነበር። በተለይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ዙሪያ ልዩ ድምቀት የነበራቸው የብስክሌት ውድድሮች ይካሄዳሉ። በርካታ ክለቦች በእነዚህ ውድድሮች በመሳተፍ ለውድድሮቹ ጥንካሬና ድምቀት በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርገዋል። ብርሃንና ሰላም፣ መከላከያ፣ ማርፌል የመሳሰሉትን በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል።
ስፖርቱ እንደ ዛሬ በየክልሉ በፌዴሬሽን ደረጃ የተከፋፈለ አልነበረም፡፡ አዲስ አበባ፣ ኤርትራ፣ ትግራይ በሚል በአንድ ብሔራዊ ፌዴሬሽን ብቻ ነበር የሚተዳደረው፡፡ በጊዜው ስፖርቱ ከመወደዱም በተጨማሪ ጠንካራና በርካታ ክለቦች ነበሩ፡፡ ያኔ የብስክሌቶች ዋጋ ውድ አለመሆኑ ለክለቦቹ መበራከት የራሱ ሚና ተጫውቷል፡፡ ይህም ስፖርቱ በመዲናይቱ ከፍተኛ እድገት እንዲኖረው አድርጓል። ክለቦቹ ጠንካራ በመሆናቸውም በአገር አቀፍ ውድድሮች ብቻ ሳይሆን በብሄራዊ ቡድን ደረጃ በመመረጥ አገርን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለማፍራት ችለዋል፡፡ በዚህ ደረጃ የነበረው ስፖርት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ መጥቷል።
አዲስ ዘመን፦ ስፖርቱን ከቀደመው ከፍታ አውርዶ ከውጤት በታች ያደረገው ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ ረዘነ፦ የስፖርቱ መዳከም በመጀመሪያ ደረጃ ከክለቦች እንቅስቃሴ ጋር የሚያያዝ ነው። እንደጠቀስኩት በወቅቱ በርካታ ክለቦች ቢኖሩም ከእነዚህ ውጭ አዲስ ክለቦች አልተፈጠሩም። ከፍላጎት ማነስም ይሁን በሌላ ምክንያት በአዲስ አበባ አዳዲስ ክለቦች ተቋቁመው የስፖርቱን ድምቀት ሲጨምሩ አልታዩም። እንዲያውም የነበሩት ክለቦች ተዳክመው መፍረስ ጀመሩ። ስለዚህ በአዲስ አበባ የብስክሌት ክለቦች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቶ እስከ መፍረስ ደርሰዋል።
በጊዜው ጠንካራ ከሚባሉት ክለቦች አንዱ የሆነው ብርሃንና ሰላም ለዚህ ትልቁ ማሳያ ነው። ምንም እንኳን ክለቡ ከ13 ዓመታት ቆይታ በኋላ እንደገና የተመለሰ ቢሆንም። በአብዛኛዎቹ ክለቦች በኩል እንደ ችግር የሚነሳው የመወዳደሪያ ብስክሌቶችና ሌሎች የስፖርቱ ግብዓቶች ዋጋ እየናረ መምጣት ነው። የብስክሌት ስፖርት ጠንካራ የፋይናንስ መሰረት ይፈልጋል። ክለቦች የመወዳደሪያ ቁሳቁሶችና ትጥቆችን በማሟላት የስፖርተኞቹን ደመወዝ በመክፈል ካምፕ ማስቀመጥ እየተሳናቸው ለመፍረስ ይገደዳሉ፡፡
ተወዳዳሪዎቹ በበኩላቸው የሚከፈላቸው ደመወዝ አነስተኛ መሆኑን በመግለፅ ራሳቸውን ከስፖርቱ ያርቃሉ፡፡ በስፖርቱ ተወዳዳሪ ሆነው የሚያገኙት ገንዘብ ህይወታቸውን ለመምራት የሚያስችል አልነበረም። አቅም ያላቸው ባለሀብቶች ክለቦችን በመመስረት ስፖርቱን ለመደገፍ ያላቸው ፍላጎት አናሳ ነው፡፡ እነዚህ ተደማምረው የብስክሌት ስፖርት አሁን ደካማ ከሚያስብለው ደረጃ እንዲገኝ አድርገዋል፡፡
አዲስ ዘመን፦ እንደ አዲስ አበባ ከተማ በአሁኑ ወቅት የብስክሌት ስፖርት ያለበት ደረጃ እንዴት ይገለፃል? ወደ ቀድሞው ዝናና ዕድገት መመለስ የሚቻል ይመስልዎታል?
አቶ ረዘነ፦ በእርግጥም እንደተባለው ከተማዋ ከዓመታት በፊት በብስክሌት ስፖርት ከፍተኛ እውቅና ነበራት። ይህ ውጤት ዳግም እንዲመጣ ጥረት ተደርጓል፡፡ የአዲስ አበባ ብስክሌት ዳግም ለማንሰራራት እንደሚችል የሚያሳዩ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች እየታዩ ነው። ከዓመት በፊት በኢትዮጵያ ሻምፒዮና አዲስ አበባ ከሁሉም ያነሰ ውጤት ይዞ ነበር የሚጨርሰው፡፡
አሁን ግን ወደ ተፎካካሪነት ደረጃ መምጣት ተችሏል፡፡ ከዓመት በፊት ሀዋሳ ላይ በነበረው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና የእኛ ልጆች እነ ፅጋቡ ገብረማርያምን ከመሳሰሉ ጠንካራ ተፎካካሪዎች ጋር በመፎካከር ተቀራራቢ ሰዓት ማስመዝገብና የብር ሜዳልያን እስከ ማግኘት ተችሏል፡፡ ይህ ውጤት ለውጦች እየመጡ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። ስለዚህ ልጆቹ ከተደገፉ በስፖርቱ ከፍተኛ ውጤት ማምጣት ይችላሉ።
አዲስ ዘመን፦ በስፖርቱ ላይ ለታየው ተስፋ ሰጨ ውጤት ምክንያቱ ምንድን ነው?
አቶ ረዘነ፦ ስፖርቱን የሚያውቁና የሚወዱ ግለሰቦች ወደ ፌዴሬሽኑ በማምጣት ቀርበው መሥራት መቻላቸው አንዱ ምክንያት ነው። አንድን ስፖርት ልደግፍ ብለህ ከተነሳህ ስፖርቱን ታሳድገዋለህ፡፡ ስፖርቱ እንዲያድግ ልባዊ መሻት አስፈላጊ ነው። የብስክሌት ስፖርቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ በስፖርቱ ያለፉትን ባለሙያዎቸ በመያዝ መሥራት ችለናል። ስፖርቱን የሚያውቁና የሚወዱን ሰዎች በማሳተፍ ፌዴሬሽኑን በማዋቀር መሥራታችን ተስፋ ሰጪ ውጤት ለመምጣት ረድቷል።
ቀደም ሲል ለስፖርተኞቹ የሚከፈለው ደመወዝ ተወዳዳሪዎቹን የሚያበረታታ አልነበረም። ተወዳዳሪ ዎቹ በየቤታቸው ነበር የሚመገቡትና የሚያድሩት፡፡ አሁን ግን ክለቦች የስፖርተኞች ማደሪያ ካምፕ አዘጋጅተው ነው የሚያሳድሯቸው፡፡ ከስፖርቱ ባህርይ ጋር የሚሄድ የአመጋገብ ሥርዓት ዘርግተዋል፡፡ እነዚህ መልካም ጅማሮዎች በስፖርቱ ቀጣይ ጉዞ ላይ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረክታሉ፡፡
አዲስ ዘመን፦ የታየውን የውጤት ተስፋ አስቀጥሎ ለመጓዝ ምን እየተሠራ ነው?
አቶ ረዘነ፦ በመጀመሪያ ደረጃ ትኩረት ያደረግነው አሁን ያሉት ክለቦች እንዲጠናከሩ የውድድር መድረኮችን ማመቻቸት ላይ ነው። ያሉትን ከማጠናከር በተጨማሪ ሌሎችን በማምጣት ክለቦችን የማስፋትን ሥራ ትኩረት ተሰጥቶታል። ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመምከር ክለብ እንዲያቋቁሙ እያደረግን ነው። የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ከ13 ዓመት በፊት አፈርሶ የነበረውን የብስክሌት ክለብ ዳግም በማቋቋም ጠንካራ ሆኖ መጥቷል።
እንደሚታወቀው ለብስክሌት ስፖርት የሚያስፈል ጉት ግብአቶች በጣም ውድ ናቸው፡፡ ግብዓቶቹን እንደ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ ስፖርቶች በቀላል ገንዘብ አሟልተህ ለማቋቋም አስቸጋሪ ነው። ክለቦችን ለማብዛት በሚደረገው ጥረት ላይ የብስክሌት ዋጋ ውድ መሆን እንቅፋት ሆኖብናል። በዚህም የተነሳ ተቋማትን በማሳመን ወደ ስፖርቱ እንዲገቡ ለማድረግ አዳጋች ሆኗል። ህብረተሰቡና አንዳንድ ተቋማት ለስፖርቱ አነስተኛ ግንዛቤ መያዛቸው እርምጃችንን አስቸጋሪ አድርጎብናል። አንዳንድ ድርጀቶችን ስናናግር እንደ እግር ኳስና አትሌቲክስ መልስ አይሰጡንም ።
አዲስ ዘመን፦ እንደ ብርሃንና ሰላም በቅርብ ጊዜ ሊመጣ የሚችል ክለብ ይኖር ይሆን?
አቶ ረዘነ፦ በብስክሌት ስፖርት ዙርያ በህብረተሰቡና በተቋማት ደረጃ ያለው እሳቤ እንደ ሌሎች ስፖርቶች አይደለም። እኛ አገር በአንድ ተቋም ውስጥ በአመራርነት ደረጃ ላይ የሚገኝ ሰው የሚፈልገው (የሚወደው) ስፖርት ብስክሌት ከሆነ ያንን ለማሳደግ ብቻ ነው የሚሮጠው። እሱ ለቆ ሌላው ሲመጣ የቀደመውን አፍርሶ ወደ ራሱ ፍላጎት ይሄዳል፡፡ እኛ አገር ለሙያውና ለስፖርቱ ሳይሆን፤ ለግለሰብ ፍላጎት ነው ጭንቁ፡፡ ወደ ተቋማት በመጓዝ ጥያቄ ስናቀርብ የሚሰጠው ምላሽ ከዚህ አንፃር የተቃኘ ነው። ስፖንሰር እንዲያደርጉና ክለብ እንዲያቋቁሙ ጥያቄ ስናቀርብ የሚሰጠን ምላሽ ይህንኑ ፍላጎት መሰረት ያደረገ ነው።
አንዳንዴ አሳዛኝ ምላሽም እንሰማለን፡፡ ‹‹ ብስክሌት ምንድነው? ምን ዋጋ አለው? የት ደርሳችኋል ?›› የሚሉ ሞራል የሚነኩ አስተያየቶችን አስተናግደናል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ፌዴሬሽኑ ያለመታከት ጥረት አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል። ጥረቱ ተስፋ አስቆራጭ ቢሆንም እንደ ቡና፣ ባንክ፣ መከላከያና አየር መንገድን ለመሳሰሉት ተቋማት ፕሮፖዛል አቅርበን መልሳቸውን እየተጠባበቅን ነው። እስካሁን ግን በክለብ ደረጃ ለመምጣት የሚችል የለም።
አዲስ ዘመን፦ ስፖርቱን በሚፈለገው ደረጃ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ላይ ያሉ መልካም ዕድሎችና ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?
አቶ ረዘነ፦ ከመደበኛ የውድድር መርሐ ግብሮች ጎን ለጎን በታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት ላይ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች እየታዩ ነው፡፡ በከተማ አስተዳደሩ ሥር በመስፋፋት ላይ ከሚገኙ ኩባንያዎችና ድርጅቶች ጋር የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ጠንካራ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ እስካሁንም ከኮካ ኮላ ኩባንያ ጋር የተደረገው ስምምነት ተጠቃሽ ነው። እየታዩ ያሉትን ተስፋ ሰጪና ጅምር ተግባራትን በማጠናከር በቀደሙት ኦሎምፒኮች ከአትሌቲክሱ ቀጥሎ አገሪቱ ትወከልበት እንደነበር የሚነገርለትን ብስክሌት ወደ ቀድሞ ስምና ክብሩ ለመመለስ የበኩላችንን ሚና እንወጣለን የሚል እምነት አለኝ።
ስፖርቱ እያሳየ ያለውን ጅምር ውጤት የፋይናንስ እጥረት ትልቁ ፈተና ነው፡፡ ስፖርቱን በከፍተኛ በጀት እያንቀሳቀሱ ከሚገኙት የትግራይና የአማራ ክልሎች ጋር ሲነፃፀር የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ይህ ነው የሚባል ጠንካራ የበጀት ድጋፍ የለውም፡፡ የፌዴሬሽኑ ዓመታዊ በጀት 180 ሺ ብር ነው፡፡ በዚህ ደግሞ የአዲስ አበባ የብስክሌት ተፎካካሪነት አቅምን የትም ማድረስ አይቻልም። ይሄንን ባገናዘበ መልኩ ፌዴሬሽኑ ጠንካራ የፋይናንስ አቅም እንዲኖረው ስፖንሰርሽፕ የማፈላለግ ሥራ በትኩረት ይሠራል፡፡
አዲስ ዘመን፦ ክለቦችን ለማጠናከርና ለማስፋፋት ከሚደረገው ጥረት በተጓዳኝ በመዲናዋ ክፍለ ከተሞች ደረጃ ስፖርተኞችን በመመልመል ታዳጊዎችን ለማፍራት የታሰበ ነገር አለ?
አቶ ረዘነ፦ እንደ አዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ታዳጊዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አቋም ተይዟል። ስለዚህ በከተማዋ ነዋሪ የሆኑ ታዳጊዎችን በፕሮጀክት ደረጃ በማቀፍ ከታች ጀምሮ ይዞ በመምጣት መሰረት ያለው ስፖርተኛ ለማፍራት ታስቧል።
ቀደም ሲል እንደ አዲስ አበባ ትልቅ ችግር የነበረውን ሴት የብስክሌት ተወዳዳሪዎችን ለማፍራት በትኩረት እንሰራለን፡፡ ቀደም ሲል የቤት ኪራይ በመክፈልና በመደጎም ሴት ስፖርተኞችን ለማፍራት ጥረት ቢደረግም የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አልተቻለም። ስለዚህ ታዳጊዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራቱ ሴት ብስክሌተኞችን ለማፍራት ያግዘናል የሚል ዕምነት አለ።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ እናመሰ ግናለን።
አቶ ረዘነ፦ እኔም አክብራችሁ ስለጋበዛችሁኝ፤ በአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሸን ስም አመሰግናለሁ።

ዳንኤል ዘነበ

Published in ስፖርት
Wednesday, 16 May 2018 17:32

ጠብ ሲል...

ቀኑን ሙሉ ስታቃጥል የዋለችው ጸሀይ ወደ አመሻሹ ቀዝቀዝ ማለት ጀምራለች።እንዲህ ሲሆን ደግሞ አብዛኛው ሰው አዋዋሉን እያስታወሰ «እፎይ» ይላል። የቀኑን ሙቀትና ጭንቀትም እያነሳ በእጅጉ ይወያያል።ሁሌም ቢሆን እንዲህ መሆኑ ተለምዷል።የእኛ ነገር ዝናብ ሲሆን ማማረር፣ ሙቀቱም ሲመጣ ያው ማማረር ነው። ይህ ደግሞ ከየወቅቱ ለውጥ ጋር ይቀያየራልና ብርቅ አይደለም።
እንዳልኳችሁ ገና በማለዳው አምርራ ስታማርር ያረፈደችው ጸሀይ ማርፈጃዋን መለስ ቀለስ ስትል ውላ ፤ ሄዳለች ሲባል ርቃ ያለመራቋን ልታሳይ የብልጭታዋን ፈገግታ ለሁሉም አዳርሳለች። የፀሃይዋን መምጣትና መሄድ በወጉ ተረዳን ያሉቱ ቀለል ያለ ልብስ ለብሰዋል። ለወትሮም ዝናብ ካላጉረመረመ መያዝ የማያስቡትን ዣንጥላ ወዲያ ጥለውም ሌጣቸውን ናቸው።
መቼም ወዳጆቼ! እንዲህ በሆነ ሰሞን እግረኛ ሆኖ አለመገኘት ነው። በተለይማ ከአውላላው መንገድ፣ ከጥርጊያው ጎዳና ንፋስ ከዛፍ ጥላ ብርቅ ሲሆን ፤ ከእመት ጸሀይ ጋር ግብግብ መግጠሙ ቀላል አይሆንም። የሰላምታ ያህል በቅኝቷ ብትጎበኝዎ አናትዎን ማዞር አይደለም ያሉበትን ቦታ ሁሉ ሊያስረሳዎ ይችላል። በውስጥዎ የሚፈጠረው ግራ አጋቢ ስሜት ነጭናጫ ያደርግዎታል።
ምንም ይሁን ምን ግን እመት ጣይቱ ማምረር ካሰበች የሚያስቆማት የለም።ከአናት እስከ እግር ጥፍር በሚዘልቅ ኃያል ጉልበቷ ያሻትን ብታደርግ ማን ሊከለክላት። በዚህ ጊዜ ማንም ምንም ማድረግ አይቻለውም። ላቡን እያንጠፈጠፈ ድካሙን ከማስታመምና እንደተለመደው ከማማረር ሌላም ምርጫ ላይኖረው ይችላል። ለነገሩ በአውላላው የጎዳና ጉዞ በጸሀይ ጉልበት ከመሸነፍ ውጭ ምን ምርጫ ሊኖር ይችላል? ምንም።
አንዳንዴ ደግሞ እንዲህ ሲያስጨንቅ የሚውለው ቀን በድንገት ባህርይውን ይቀይርና ደርሶ ግራ ያጋባል። ዳመናው በሰማይ ሳይታይ ከየት መጣ የማይሉት ዝናብ ዶፍ አስከትሎ ያጥለቀልቃል። ይሄኔ ታዲያ መንገደኛውም ይሁን ከቤት ያለው የሚይዝ የሚጨብጠውን ያጣል። ድንገቴው ዝናብ ቃጠሎውን አባሮ ሁሉን ማተራመስ ሲይዝ ድንግርግሩ አጀብ ያሰኛል።
በዚህን ጊዜ ከቤት የዋለው ከደጅ የተወውን ሊያስገባ፣ ከውጭ ያሰጣውን ሊሰበስብ ሩጫና ጥድፊያው ያይላል።በዚህ አጋጣሚ ሁሉም የኔ የሚለው አጣዳፊ ጉዳይ ይኖረዋልና ለሌላው እገዛ ላይደርስ ይችላል። ሌላውም ቢሆን ከዝናቡ ድንገቴ ጥፋት እንዲታደጉት የጎረቤቶቹን አስቸኳይ እርዳታ አይፈልግም።ያለ የሌለ ሀይሉን ተጠቅሞ በዝናብ የሚበላሹ ቁሶችን በጥድፊያ ይሰበስባል። ይህ የሚሆነው ግን ምንአልባት ዝናቡ የአፍታ ጊዜ ከሰጠውና የመታገስ ምልክት ካሳየው ብቻ ነው።
መቼም ይህኛው እውነት ድንገቴው አጋጣሚ የፈጠረው ክስተት ነው ይባል።እንዲህ ከሆነ አጋጣሚው የሚያስከትላቸው የተለመዱ ለውጦች ከተጠቃሚው እርምጃ ጋር ሊታዩ ይችላሉ። እኔ ግን ሁሌም ቢሆን ግርም የሚለኝ ሀይለኛ የሚባል ዝናብ ጥሏል በተባለ ቀን የሚከሰተው ችግር ብቻ አይደለም። ለእኔ አስገራሚውና አናዳጁ ጉዳይ ጥቂት ዝናብ ጠብ ሲል በከተማው የሚታየው የባህርይ ለውጥ ነው።
ወዳጆቼ! አበው ሲተርቱ «ክፉ ቀንን አያምጣ» ይላሉ። እነሱ እንዲህ ለማለታቸው የራሳቸው የሆነ ብዙ ምክንያት ይኖራቸዋል። እኛ የአባባሉን ስጋት እንገምት ከተባለ ደግሞ በርካታ እውነታዎችን ልንመዝ እንችላለን። እውነት እኮ ነው! እንዲህ አይነቱ ክፉ የሚባል ቀን ሲመጣ የሚሆነው አይታወቅም። ደግ የተባለው ክፉ፣ቀና የነበረው ጠማማ፣ነጩ ጥቁር፣ ሜዳውም በአንዴ ገደልና ሸለቆ ሊሆን ይችላል።
«ትንሽ ደግስና ወዳጅ ጠላትህን ለይ» እንዲሉ እንዲህ አይነቱ ቀን ሲያጋጥም ጥሬውን ከብስሉ ለመለየት ያመቻል። በዚህ ጊዜ ማን በጎ እንዳሰበ ፣ ማንስ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ሽንቁር እንዳሰፋ ለማወቅ ቀላል ነው።አያልፉት የለምና ይህ ቀን አልፎ በትውስታ ሲያወጉት ደግሞ የትዝብትና የምስጋናው ነገር መሳ ለመሳ ሆኖ በአንድ መወጋቱ አይቀሬ ነው።የዛኔ ታዲያ በክፉ ቀን ክፉ የሰራውን ሆኖ አለመገኘት ነው።
የከተማችን አንዳንድ ባለታክሲዎች ጉዳይም ልክ እንደዛው ማለት ነው።ዶፍም ይሁን ጠብታ ለአፍታ መጥቶ መመለሱ ላይቀር ፣ከበረዶም በኋላ ጸሀይ ደምቃ «አለሁ»ማለቷን ላትተው፣ በሰዎች ልቦና ክፉ ስማቸውን እንዳፃፉ ያልፋሉ፡፡ ሁሌም ትዝብትን አትርፈው ይጓዛሉ፡፡
ቀኑን ጸሀይ ውሎ ጥቂት ዝናብ ጠብ ባለ ቁጥር ለእንዲህ አይነቶቹ ልማደኞች መልካም የሚባል አጋጣሚ ይሆናል። ሰበብ ፈላጊዎቹ ጠዋት እየለመኑ ሲያሳፍሩት የነበረውን ሰው እንደማያውቁት ሆነው በራቸውን ይዘጋሉ። የታክሲ ሾፌሮች ድርጊት ታክሲ ፈላጊው ሲንገላታና ሲሯሯጥ ማየትም በእጅጉ የሚያስደስታቸው ይመስላል። በዚህ ወቅት እነዚህ አሽከርካሪዎች ቢጠሯቸው አይሰሙም። የዝናቡ ጠብታ ለኪሳቸው ጥሩ ሲሳይ እንደሚያመጣ በማሰብ በነባሩ ታሪፍ ላይ በእጥፍ ጨምረው ይደራደራሉ። በዕለቱ ማንም ቢለምናቸው፣ ቢያለቅስና ቢያዝን ደንታቸው አይደለም። ባዶውን ታክሲ በኩራት እያሽከረከሩ ማለፍም የተለመደ ድርጊታቸው ሆኗል፡፡
አንዳንዶቹ በጉጉት አፍጥጦ በሚጠብቃቸው እግረኛ መሀል ሰንጥቀው ሲያልፉ የሚያሳዩት ያልተገባ ድርጊት ደግሞ ያስገርማል፣ያሳዝናል፤ያናድዳል። የመጡበትን ፍጥነት እንደማቀዝቀዝ አድርገው ቆም ለማለት ይሞክራሉ። ይህኔ ሊያሳፍሩን ይሆናል በሚል ጉጉት የሚሽቀዳደመው ተሳፋሪ የታክሲውን በር አንቆ አብሮ መሮጥ ይጀምራል። እንዲህ ሲሆን የእነሱ ትምክህት አብሮ ይጨምራል።በሩጫ እየተከተለ የከበባቸውን ሰው የኋሊት እያዩም «አንሄድም» ይላሉ።
አሁንም መሮጥና መጓጓት የማይደክመው የሩቅ ሰፈር ነዋሪ ከሩቅ ብቅ የሚለውን ታክሲ እየጠበቀ በሩን አንቆ ይሽቀዳደማል። አሁንም ግን ከተመሳሳይ ልፋትና ጉጉት በኋላ « አይሄድም» በሚል ምላሽ ይሸኛል። በዚህ ጊዜ የአንዳንድ ባለባጃጅ አሽከርካሪዎች ባህርይም በጣም የሚገርም ነው፡፡ ቀኑን ሙሉ ሲመላለሱበት የሚውሉበትን መንገድ በተለየ ሁኔታ ተመልክተው «ኮንትራት ካልሆነ አንሞክረውም» ይላሉ።
ወዳጆቼ! በጠራራ ጸሀይ ድንገት ጠብ የምትል ዝናብ ምንያህል ለውጥ ታመጣ መሰላችሁ? ግን እንደአበው ተረት ክፉ ቀን አያምጣ እንጂ ከዚህ የባሰ አጋጣሚ ቢፈጠር ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመቱ ቀላል ነው። ያም አለ ይህ ግን ዝናቡ ሲያልፍ ጸሀይ፣ ጨለማው ሲነጋም ብርሀን መተካቱ አይቀርምና ለሚያልፍ አጋጣሚ ክፋትን አንልመድ እላለሁ። ባህርያችን ከወቅት ጋር ሊቀያየር አይገባምና፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

Published in መዝናኛ

ተደጋግሞ እንደሚባለው ማንኛውም ሰውና የተሰማራበት  የስራ  ዘርፍ  ክቡር  ነው። የትኛውም ባለሙያ በተሰማራበት  ሙያ  ራሱንንና ቤተሰቡን ከመምራት ባለፈ ለሙያው ስነምግባር ተገዢ መሆኑም ማንነቱን እንዲያስከብር ያደርገዋል። አንዳንድ ጊዜ ግን የስራን ክቡርነት አቅልለው የሚያዩ በርካቶች በስራ ላይ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ያነሰ ክብርና ግምት እንዳላቸው ይስተዋላል።ለእንዲህ አይነቱ እውነታ ቅሬታቸውን የሚገልጹት  የጽዳት ሰራተኞችም በሙያቸው ዙሪያ የአንዳንድ ተጠቃሚዎችን በጎ ያልሆነ ድርጊት እንደማሳያ ይጠቅሳሉ።የአዲስዘመኗ መልካምስራ አፈወርቅም በጽዳት ሙያ የተሰማሩ ባለሙያዎችን ህይወትና የስራ ላይ ፈተናዎችን በተመለከተ ከጉዳዩ ባለቤቶች ያገኘቸውን ተሞክሮ «እነሆ» ብላናለች። 

 

ሌቱ አልፎ ንጋቱ ሲቃረብ፣ በዕንቅልፍ የደከሙ ዓይኖቿ ይነቃሉ። በነጋ አልነጋ ጭንቀት ሲባትት ያደረው አካሏም ለጉዞ ፈጥኖ ይዘጋጃል። ከቤት ርቃ መንገድ ለመጀመር ግን እግሮቿ በኩራት አይራመዱም። ከሞቀ መኝታዋ ወጥታ ከጎዳናው ስትገባ አይኖቿ ሌሎች መንገደኞችን ያማትራሉ። ሁሌም ቢሆን ለብቻዋ መጓዝን አትደፍርም። እሷ ድንገቴ ኮሽታ ያስደነግጣታል። የጨለማውም ግዝፈት ያስፈራታል። እናም አብሯት የሚራመድ እስክታገኝ ድረስ የእግር ኮቴ ስታዳምጥ ትቆያለች።
አንድ ቀን ወይዘሪት የሺ መኩሪያ ከቀበና አካባቢ ወደ ውስጥ አልፎ ከሚገኘው መኖርያ ቤቷ ማልዳ ወጣች። የዚያን ዕለት ጨለማው በወጉ አልገፈፈም። መንገዱም ገና አልተጋመሰም። ይሄኔ ልቧ በድንጋጤ መምታት ጀመረ። ፍርሀት ይወራት፣ ያንቀጠቅጣት ያዘ። ፊትና ኋላዋን እየቃኘች መንገዷን ቀጠለች። በዚህ መንገድ ብዙ ክፉ አጋጣሚዎች እንዳሉ ታውቃለች። ሌቦች ወጪ ወራጁን ጠብቀው ይዘርፋሉ፣ ይደበድባሉ። የነጋባቸው ጅቦችም ወደ ጫካቸው ሲገሰግሱ ሰዎችን ይተናኮላሉ። የሺ እነዚህንና ሌሎች ወሬዎችን ሰምታለች።
ወጣቷ በአዕምሮዋ ብዙ ሃሳብ ይመላለሳል። መስሪያ ቤቷ ከሌሎቹ ሠራተኞች ቀድማ መድረስ አለባት። ሥራ ቦታዋ አይቀሬው ግዴታ ይቆያታል። ብርድና ዝናብ፣ ጨለማና ጭጋግ ለእሷ መሰሉ ሠራተኛ ሰበብ አይሆንም። በሰዓቱ ተገኝታ ግዴታዋን መወጣት አለባት። እሱን ከውና ስታጠናቅቅ ደግሞ ጤና አጥተው አልጋ ላይ ለዋሉት እናቷ መድረስ ይኖርባታል።
የፅዳት ሠራተኛዋ ይህን ሁሉ እያሰበች ወደ ፊት ተጉዛለች። በመንገዷ አጋማሽ አብሯት የሚዘልቅ መንገደኛ እንደሚገጥማት ገምታለች። አሁን ገና ከዋናው መንገድ አልደረሰችም። የመንደሩን እጥፋት ጨርሳ ከአስፓልቱ እስክትገባ ሰፈሩ ሁሌም እንዳስፈራት ነው። የሺ ድንገት ኮሽታ ቢጤ የሰማች መሰላት። ከጀርባዋ የሚከተላት እንዳለም ገመተች። አጠገቧ እስኪደርስ ማንነቱን አላወቀችም። ከኋላዋ የደረሱ ስፖርተኞች ግን ፈጥነው ለዩትና ወደእሷ ሳይቀርብ እያዋከቡ መለሱት። ቆይታ የሺ የሆነውን ሁሉ ተረዳች። እሷን ሲከተላት የቆየው መንገደኛ ሰው ሳይሆን አያ ጅቦ መሆኑን አወቀች።
ይህ ካጋጠማት በኋላ የሺ ለብቻዋ ከቤት መውጣት አትደፍርም። ሰዎች ሲበራከቱና መንገዱ በእግረኞች ሲያዝ ጠብቃ አብራ ትጓዛለች፡፡ የሰፈሯን ስጋት በዚህ ዘዴ አዋዝታ ከመስሪያ ቤቷ ስትገባ እሷን የሚጠብቀው የፅዳት ሥራ ከነብዙ ችግሮቹ ይቀበላታል። የሥራ ልብሷን ቀይራ መጥረጊያና መወልወያዋን በመያዝ ለዕለት ሥራዋ ትሰለፋለች፡፡ የምታየውን እንዳለየች ሆናም ኃላፊነቷን በጥንካሬ መወጣት ትጀምራለች።
ወጣቷ ከሦስት ዓመታት በላይ በዘለቀችበት የፅዳት ሥራ ብዙ ተፈትናለች። ሙያዋን አክባሪ ብትሆንም የሥራዋ ባህርይና የአንዳንድ ሰዎች ድርጊት ያሳደረባት አሉታዊ ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። የሺ የማለዳውን ውጣ ውረድ አልፋ ወደ ሥራ ስትገባ የመጀመሪያ ተግባሯ መፀዳጃ ቤቶችን መጎብኘት ነው። በዚህ ቦታ ለዓይን የሚከብዱ ለመናገርም የሚቸግሩ ድርጊቶች ያጋጥሟታል።
የሺ ሁሌም ለሥራ ወደ ውስጥ ስትዘልቅ የአንዳንድ ሰዎች የመፀዳጃ ቤት አጠቃቀም ልምድ ያስገርማታል። አብዛኛዎቹ ከተጠቀሙ በኋላ ውሃ የመልቀቅ ፍላጎቱ የላቸውም። ከተገቢው ቦታ ይልቅ በወለል ላይ የመጠቀምና አካባቢውን የመበከል ልምድ ተክነዋል። ጥቂት የማይባሉት ደግሞ በግርግዳዎች ላይ ቆሻሻን በማኖር አስጸያፊ ድርጊት ይፈጽማሉ።
ይህን ያልተገባ ልምድ ለመጠቆም ደግሞ እሷና ባልደረቦቿ «እባካችሁ» ሲሉ በማስታወቂያ መልክ ለማሳሰብ ሞክረዋል። አብዛኛዎቹ ለማሳሰቢያው «ጆሮ ዳባ ልበስ» ማለታቸው አሁንም ድረስ የቢሮ አካባቢዎች በመጥፎ ሽታና በቆሻሻዎች እንዲበከሉ እያደረገ ነው። ከዚህ ባለፈ ‹‹ሰዎች ስለሰዎች ማንነት ሊጨነቁ ይገባል›› የምትለው የሺ ይህን የሚያደርጉት ሰዎች ድርጊቱ በእነሱ ላይ ቢደርስ ምን እንደሚሰማቸው በማሰብ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ትናገራለች፡፡
በፅዳት ሥራ ቆይታዋ የበርካቶችን ያልተገባ ልማድ አስተውላለች። ሁሌም ለፅዳት ስትሰማራ ከሚያጋጥማት በእጅ ከቆሸሸ አካባቢ ሌላ በፊት መታጠቢያ ሳህኖች (ሲንኮች) ላይ የምታገኘው የጫማ ጭቃና የጸጉር እጣቢም ዘወትር እንድታዝን ያደርጋታል። እንደውም አንዳንዴ በመፀዳጃ ሳህኖች ላይ ከነጫማቸው ወጥተው የሚጠቀሙ ሰዎች ያጋጥሟታል። እነዚህም ቢሆኑ ትተውት ለሚሄዱት የጫማቸው ጭቃና አቧራ የማይጨነቁና ለሌሎች ሰዎች ደንታ የሌላቸው ናቸው።
የሺ አሁን ያለችበት መስሪያ ቤት ተቀጥራ ከመግባቷ በፊት በሌሎች ቦታዎችም ግቢ በማስዋብና በአትክልተኝነት ሥራ ላይ ቆይታለች። በቋሚነት መደብ ለፅዳት ሥራው ተወዳድራ ስትገባና የወር ደመወዝተኛ ስትሆንም በእጅጉ ተደስታ ነበር። አሁንም ቢሆን በሥራው ክቡርነት ታምናለች። ስለነገ ማንነቷም መሰረት ለመጣል ያቋረጠችውን ትምህርት የመቀጠል ዓላማዋን ሰንቃለች።
ወይዘሮ ማህሌት በቀለም በመስሪያ ቤት የፅዳት ሙያ ላይ ከሦስት ዓመታት በላይ ቆይታለች። ተቀጥራ ለምትሠራበት ሙያ ኃላፊነቷን የምትጀምረው ገና ከማለዳው አንስቶ ነው። ወይዘሮ ማህሌት ልክ እንደየሺ ሁሉ አራት ኪሎ በሚገኘው መስርያ ቤቷ በሠዓቱ ለመገኘት በጠዋቱ መነሳት ግድ ይላታል። እንጦጦ ኪዳነምህረት አካባቢ ከሚገኘው መኖርያ ቤቷ ወደ መስርያ ቤት ለመሄድ ሁሌም በጠዋት ጉዞ ትጀምራለች፡፡ ባሰበችው ሰዓት ተነስታ ለመጓዝ ግን አካባቢው በጫካ የተከበበ መሆኑ ስጋት እንደፈጠረባት ነው፡፡ በዚህ አካባቢ ማልዶ የሚገሰግስ የቀማኞችና የአውሬዎች ሲሳይ ሊሆን እንደሚችል ትናገራለች፡፡
ወፍ ሲንጫጫ አንስቶ እግሮቿን ለጉዞ የምታሰላው ወይዘሮ ብዙዎች ጉዞ መጀመራቸውን ስታረጋግጥ ከቤቷ ትወጣለች። ይህን ከማድረጓ በፊት ግን የእናትነት ግዴታዋ ወደ ኋላ ይመልሳታል። ገና አንድ ዓመት የሞላትን ልጇን በወጉ አጥብታና አለባብሳ ለጎረቤት አደራ መስጠት አለባት። ደርሳ እስክትመለስና የሰጠችውን እስክትቀበልም ልቧ ለሁለት ይከፈላል።
ወይዘሮ ማህሌት በፍጥነት ገስግሳ የምትሄድበት ቢሮ ስትደርስ ሥራዋን የምትጀምረው መፀዳጃ ቤቶችን በማፅዳት ነው። ብዙ ጊዜ ገና ከበሩ የሚቀበላት መጥፎ ሽታ ወደ ውስጥ ስትዘልቅ ለዓይን ከማይመች እይታ ጋር ያገናኛታል። እሷ ለሙያዋ የተለየ ክብር ያላት መሆኑ ሥራዋን በአግባቡ እንድትወጣ አላገዳትም። ይሁን እንጂ በየቀኑ የምታየው ያልተጋባ ድርጊት አንዳንዶችን እንድትታዘብና በተግባራቸው እንድታፍር አድርጓታል።
ከአንድ ዓመት በፊት ነፍሰጡር በነበረችበት ጊዜ ደግሞ የምትመለከተው ቆሻሻና ለአፍንጫዋ የሚደርሰው መጥፎ ሽታ ለእሷ እንደማይስማማ ታስታውሳለች፡፡ ይሁን እንጂ እንደምንም ከራሷ ጋር ታግላና የውስጧን ስሜት አሸንፋ ቀኗን በድል ስትወጣ ቆይታለች። ለእሷ ይህ አጋጣሚ ፈታኝ የሚባል ቢሆንም ከማንነቷ ይልቅ የሙያ ግዴታዋን በማስቀደሟ ሥራዋን በብቃት ተወጥታለች።
ዛሬም ይሁን ትናንት ግን ለፅዳት ባለሙያዋ ወይዘሮ ማህሌት እጅግ የሚያሳዝናት አንድ እውነት አለ። ሁሌም የአንዳንድ ሰዎች ያልተገባ ልማድ እንደባህል ሆኖ መቀጠሉ በእጅጉ ያስገርማታል፡፡ በየቀኑ በየመፀዳጃ ቤቶቹ የሚታየው የአጠቃቀም ችግር አለመሻሻሉ ያሳስባታል። ከቢሮ እስከ መፀዳጃ ቤቶች በምታደርገው የፅዳት ሥራ ፈታኝ ነገሮች ገጥመዋታል። አንዳንዶች በመፀዳጃ ቤቶች አካባቢ የሚተገብሩት አሳፋሪ ድርጊት ሁሌም ይዘገንናታል፡፡
በመጸዳጃ ቤቶች ውስጥ በአግባቡ መወገድ የሚገባቸው ቆሻሻዎች እንደነውር ሳይቆጠሩ በየሜዳው ይጣላሉ። በተለይ አንዳንድ ሴቶች በንጽሕና መጠበቂያ ቁሶች ላይ ያላቸው የአወጋገድ ልማድ እጅግ ደካማ ነው። ብዙ ጊዜም በእጅ መታጠቢያዎችና በመመላለሻ ወለሎች ላይ ለዓይን የሚከብዱ ድርጊቶች ተፈጽመው ማስተዋሏ ከሰው ልጆች የማይጠበቅ ነውና አሁንም ያሳዝናታል። እንዲህ ዓይነቱን ያልተገባ ድርጊት ከሚፈፅሙ ሰዎች የሚሰነዘረው አስተያየት ደግሞ ያስገርማታል፡፡ እነሱ በየቀኑ ለእንዲህ ዓይነቱ ነውረኛ ድርጊት ሳይታክቱ አንድ ቀን እንከን ሲያገኙ የፅዳት ባለሙያዎችን ለመውቀስና ለመክሰስ ይሯሯጣሉ፡፡
አንዳንዴ ደግሞ በቢሮ ያሉ ሠራተኞች በጠረጴዛቸው ላይ የሚያፈሱት ሻይና የሚያንጠባጥቡት ምግብ ለፅዳት የሚያዳግትበት ጊዜ ይኖራል። ይህን በተመለከተም ብዙዎች ምክርና አስተያየት ለመቀበል ቀና አይደሉም። ሁሉንም ሠራተኛ እንደባህርይው አቻችሎ የማደር ልማዱ እንዳላት የምትናገረው ወይዘሮ ማህሌት የሥራ ግዴታዋ ጥንቃቄን ከታላቅ ኃላፊነት ጋር እንድትለምድ አድርጓታልና በዚህ ትደሰታለች።
ማንም ሰው የሚጠቀምበትን ንብረት እንደራሱ በመቁጠር ሊጠነቀቅለት እንደሚገባ ወይዘሮ ማህሌት ታምናለች። የፅዳት ሙያን ሥራዬ ብለው ለያዙ ሠራተኞች ደህንነትም ማሰብ ታላቅነትን ያሳያል ባይ ነች። ‹‹ማንም ቢሆን በሰውነቱ ክቡር ነው›› የምትለው ወይዘሮዋ ማሰብና መተሳሰብ ካለ ችግሮችን እየፈቱ ለመጓዝ መንገዱ ቀና እንደሚሆን በእርግጠኝነት ትናገራለች። ማህሌት ዛሬ ባለችበት ሙያ ላይ የመቀጠል ሃሳብ የላትም። ለዚህ ውጥኗ ደግሞ ራሷን በትምህርት አሳድጋና ማንነቷን ለውጣ በተሻለ ዕድገት መጓዝ ትፈልጋለች፡፡
እንደ የሺና ወይዘሮ ማህሌት ሁሉ በርካቶች በተሰማሩበት የፅዳት ሙያ ላይ በሚያጋጥማቸው የተጠቃሚዎች እንከን ሳቢያ ሁሌም ቅሬታቸውን ያሰማሉ። እውነት ነው! በቀላሉ መጠቀምና ለሌሎች ማሰብ እየተቻለ በአጉል መዘናጋት የሚመጣው ልማድ ጉዳቱ ለሁሉም መሆኑ አይካድም። የፅዳት ሠራተኞቹ መጥረጊያና መወልወያ ቆሻሻውን ለማፅዳት ቢያግዛቸውም፤ የሰዎችን ያልተገባ ድርጊት ለማስተካከል ግን አላስቻላቸውም፡፡ አንዳንዶች የቆሸሸውን ልማዳቸውን በመልካም አመለካከትና ሥርዓት ሊያፀዱት እንደሚገባ አጥብቀው ያሳስባሉ፡፡ እስቲ ሁላችንም ወደ ራሳችን በመመልከት ልምዳችንን እንቃኝ። በተለይም የመጸዳጃ ቤት አጠቃቀምና ቆሻሻን የማስወገድ ልምዳችንን በመፈተሽ ራሳችንን መገምገም ይገባል፡፡

 

Published in ማህበራዊ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር በ2008 ዓ.ም በሰራው ሂሳብ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ጉድለቶች ማግኘቱን አስታውቆ ነበር፡፡ በኦዲት ግኝቱ የሂሳብ አሰራርን የተላለፉ፣ ያልተሰበሰቡ፣ የተጓደሉና ሌሎች ህጸጾችን ዩኒቨርሲቲው እንዲያስተካክል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ሚያዝያ 15 ቀን 2010 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት እና የዲላ ዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎች የተወሰደውን ማስተካከያ ገምግመዋል፡፡
በጥሬ ገንዘብ ቆጠራ ወቅት 37ሺ 900 ብር በመብለጥ የተገኘበት ምክንያት አለመታወቁ፣ ከልዩ ልዩ የገቢ ምንጮች የተሰበሰበ ሁለት ሚሊዮን 833ሺ 280 ብር ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሪፖርት አለመደረጉ በመደበኛ ሰዓት ሊሰሩ የሚገባቸው ስራዎች በኮንትራት መሰራታቸው፤ የትርፍ ሰዓት፣ የማበረታቻና የአስተባባሪነት በሚል የሚመለከተው አካል ሳይፈቅድ አምስት ሚሊዮን 846ሺ 079 ብር መከፈሉ በኦዲት ግኝት መረጋገጡን ቋሚ ኮሚቴው አንስቷል።
በህጉ መሰረት ትክክለኛ ደረሰኝ መጠቀም እየተገባ ዩኒቨርሲቲው በዱቤ ሽያጭ የአምስት ሚሊዮን 413ሺ 691 ብር ግዥዎችን ፈጽሟል። በዩኒቨር ሲቲው ዋና ግቢ 504ሺ 084 ብር በወጪ ተመዝግቦ ሳለ በድጋሚ ለጤና ሳይንስ ኮሌጅ በዝውውር ተከፍሏል። ለዩኒቨርሲቲው ግንባታ ከሚያከናውኑ ዘጠኝ ሥራ ተቋራጮች እና ውል ገብተው በወቅቱ እቃ ካላቀረቡ ድርጅቶች ዘጠኝ ሚሊዮን 701ሺ 565 ብር አልሰበሰበም፡፡
በጨረታ መገዛት ሲገባው ህግ በመተላለፍ በቀጥታ ግዥ እና ከተቀመጠው የግዥ ጣሪያ በላይ በዋጋ በማወዳደር በድምሩ ሶስት ሚሊዮን 261ሺ 865 ብር ወጪ ተደርጓል። በ2008 በጀት ዓመት ሊሠሩ ከታቀዱ ሥራዎች በጀት ዓመቱን ያልጠበቀ የ30 ሚሊዮን 113ሺ 316 ብር ግዥ ተከናውኗል፡፡ በኦዲት ናሙና ከተመረጡ ሰነዶች ውስጥ ስድስት ሚሊዮን 873ሺ 851 የያዙ የ16 የክፍያ ሰነዶች ለኦዲት አለመቅረ ባቸውንም ቋሚ ኮሚቴው አንስቷል።
በግዥ መመሪያው ለተጨማሪ ግንባታ ቀደም ሲል ከተገባው ውል ከ25 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት ቢያስቀምጥም ለዩኒቨርሲቲው ስብሰባ አዳራሽ ተጨማሪ ዕድሳት መከፈል የሚገባው 274ሺ 696 ብር ሆኖ ሳለ አራት ሚሊዮን 720ሺ 701 ብር ተከፍሏል። ለግንባታ የሚፈፀመው ክፍያ በአማካሪ መሀንዲስ በሚሰጥ የስራ አፈጻጸም ምስክርነት መሆን ሲገባው፤ ለ21 የግንባታ የስራ ተቋራጮች እና ጂ አይ ዜድ ለተባለ ድርጅት የምስክር ወረቀት በአማካሪው ሳይረጋገጥ እና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የተደረገ የውል ሰነድ ሳይቀርብ 44 ሚሊዮን 36ሺ433 ብር ከመመሪያ ውጪ ክፍያ ተፈጽሟል።
ትምህርት ሚኒስቴር ሲያሰራቸው ከነበሩ ተቋራጮ ወደ ዩኒቨርሲቲው ገቢ የሆነውን 16 ሚሊዮን 501ሺ 754 ብር ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በወቅቱ ፈሰስ አላደረገም። በውጭ አገር አስተምሯቸው በውላቸው መሠረት ካላገለገሉት ግለሰቦች ላይ መሰብሰብ የሚገባውን 142ሺ 740 ብር ገቢ አላደረገም። አንድ መምህር ደግሞ ውል ሳይፈጽም ለትምህርት ወደ ውጭ አገር እንዲሄድ መደረጉም ተመልክቷል፡፡
በተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳብ በኩል ከአንድ እስከ 14 ዓመት የቆዩ ስምንት ሚሊዮን 405ሺ 369 ብር በወቅቱ እንዲወራረድና እንዲሰበሰብ አለመደረጉ፣ በኮንትራት መያዣነት 12 ሚሊዮን 784ሺ 647 ብር የግዴታ ውል ተገብቶባቸው በወቅቱ አለመወራረዳቸው፤ ከውስጥ ገቢ፣ ከካፒታል እና ከመደበኛ በጀት 32 ሚሊዮን 255ሺ 614 በዕቅዱ መሰረት አለመፈጸሙ ተነስቷል፡፡
ከንብረት አስተዳደርና አወጋገድ ጋር በተያያዘ በአንድ ሚሊዮን 720ሺ 500 ብር የተገዙ ዕቃዎች በቴክኒክ ኮሚቴ ሳይረጋገጡ ገቢ ተደርገዋል፡፡ እንዲሁም በሶስት ሚሊዮን 184ሺ ብር የተገዙ ጤፍና ማርማላት ወደ ንብረት ክፍል መግባታቸውን የሚያረጋግጥ የገቢ ደረሰኝ በኦዲት ወቅት አልቀረበም። ከ2006 እስከ 2008 በጀት ዓመት ርክክብ የተፈፀመባቸው ህንፃዎች እና መኖሪያ ቤቶች በቋሚ ንብረት አልተመዘገቡም። የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው የቤተ ሙከራ ኬሚካሎችና መድኃኒቶች አለመወገዳቸው፤ በርካታ ወንበሮችና 25 ተሽከርካሪዎች ተጠግነው አገልግሎት እንዲሰጡ ወይም እንዲወገዱ አለመደረጋቸውም ተጠቅሷል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የሥጋት ተጋላጭነት የዳሰሳ ጥናት አለማድረጉም በኦዲት ግኝቱ ተመላክቷል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር በ2006 እና 2007 በጀት ዓመት የሂሳብ ግኝቶች ላይ የዋና ኦዲተር የማሻሻያ ምክረ ሃሳቦችን ተቀብሎ የዕርምት እርምጃ አለመውሰዱን ጠቁሟል፡፡ ለ2008 በጀት ዓመት የኦዲት ግኝትም በአብዛኛው ምላሽ እንዳልሰጠ ተመልክቷል፡፡ የዩኒቨርሲቲው አመራር በባለቤትነትና በተጠያቂነት ኃላፊነቱን የማይወ ጣበት፤ ለመንግስት ደንብና መመሪያ ተገዥ የማይሆንበትን መሠረታዊ ምክንያት እንዲያብራራ ቋሚ ኮሚቴው ጥያቄ አቅርቧል፡፡ በተነሱት የሂሳብ ግኝቶች ላይ የተወሰደውን የእርምት እርምጃ እንዲያስረዳም ተጠይቋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ቃልኪዳን ነጋሽና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በሪፖርቱ በመብለጥ የተገኘው 37ሺ 900 ብር ለሪፈራል ሆስፒታል ሰራተኞች ሊከፈል የተዘጋጀና በእለቱ ለሰራተኞቹ መከፈሉ አስፈላጊ ማስረጃዎችን በማቅረብ ከዩኒቨርሲቲው የውስጥ ኦዲት ጋር መግባባት ላይ መደረሱን ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ በማነስ ሪፖርት የተደረገው ገንዘብ ለህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅና ለሪፈራል ሆስፒታል መድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎች ከዕቅድ በላይ በመገዛታቸው ለተፈጠረው የገንዘብ እጥረት የተጠቀሰው ገንዘብ ፈሰስ ሳይደረግ አሰራሩን ጠብቆ ለዩኒቨርሲቲው ወጪ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ኃላፊዎቹ እንዳሉት አላግባብ የተከፈሉ ክፍያዎችና ጥቅማ ጥቅሞች በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተቋርጠዋል። ከሥራ ባህርያቸው አንፃር የትርፍ ሰዓት ክፍያ የሚያስ ፈልጋቸው የሥራ ክፍሎች ተለይተው ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ከፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስቴር በተገኘ ፈቃድ መሰረት እየተከፈለ ነው፡፡ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በመምጣት በማማከርና በማስተባበር የሚሰሩ መምህራንና በድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች የሚከፈሉ ክፍያዎችን ማቆም በትምህርት ስራው ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ስላለው በአስተዳደር ካውንስሉ ፀድቀው የነበሩ ክፍያዎች ዝርዝር ጥናት ተደርጎባቸው በቦርድ እንዲፀድቁ ይደረጋል ብለዋል፡፡
በወቅቱ በፋይናንስ የስራ ክፍል የሠነድ አያያዝ ችግር ደጋፊ ማስረጃ ያልቀረበለትና በዱቤ ሽያጭ የተወራረደ ሂሳብ አሁን ደጋፊ ማስረጃዎች መቅረባቸውን ነው ኃላፊዎቹ ያስረዱት፡፡ አላግባብ የተመዘገበው ሂሳብ በሂሳብ ሰነድ ወይም ፋይናንሻል ስቴትመንት ላይ ስለተዘጋ በቀላሉ በዩኒቨርሲቲው የሚፈታ ባለመሆኑ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ድጋፍ እንዲደረግ ጥያቄ ቀርቦ ባለሙያ እስኪላክ እየተጠበቁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ኃላፊዎቹ እንዳሉት፤ አብዛኛዎቹ የግንባታ ፕሮጀክቶች ባለመጠናቀቃቸው ወደ ጉዳት ካሳ ጥያቄ ደረጃ አልተደረሰም፡፡ ፕሮጀክቶቹ የሚዘገዩት በዩኒቨርሲቲውና በአማካሪ ድርጅቶች ችግር ጭምር በመሆኑ ሥራ ተቋራጮችን ብቻ ለመጠየቅ አመቺ አልሆነም፡፡ በቀጥታና በዋጋ ማወዳደሪያ የተፈፀመው ግዥ የውሃ መሳቢያን (ፓምፕ) ለመሳሰሉ አጣዳፊ ችግሮች ምላሽ ለመስጠት ነው። የግዥ ችግሮች ከአሰራር ጋር የተያያዘ መሆኑ በግምገማ በመረጋገጡ የግዥ ዳይሬክተሩን በመቀየር ከ2009 ዓ.ም የግዥ ሥርዓቱ የተሻለ ሆኗል፡፡
የተማሪዎች የመፀዳጃና መታጠቢያ ቤቶች እጥረት ስለነበር በወቅቱ አዲሱ የዩኒቨርሲቲው አመራር ችግሩን ለመቅረፍ ከእቅድ ውጪ ግዥ ማከናወኑ ተመልክቷል፡፡ እንደ ጄኔሬተር ያሉ አንገብጋቢ ግዥዎች መፈፀማቸው እና ከበጀት ዓመት የተሻገሩ ክፍያዎች መኖራቸውንም ኃላፊዎቹ ተቀብለዋል፡፡ የተማሪዎች የምግብ አቅርቦት ከጨረታ በኋላ በሚከሰቱ የዋጋ ጭማሪዎች እና ሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ክፍያው ለውጥ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው 29ኛውን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉባኤ እንዲያስተናግድ በመመረጡ ደረጃውን የጠበቀ አዳራሽ መገንባት በማስፈለጉ ለስብሰባ አዳራሹ ተጨማሪ ክፍያ መፈፀሙ በኃላፊዎቹ ተመልክቷል፡፡ ይህም በመመሪያው ከተፈቀደው ጣሪያ በላይ ክፍያ እንዲወጣ አድርጓል፡፡ የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ለመጀመሪያው የህንፃ እድሳት ግዥ ፈቃድ በመስጠቱ ተጨማሪ ስራውን ሳያስፈቅድ ጥገናው መካሄዱ ስህተት መሆኑን ጠቁመው ጥፋቱን በፈጸመው የቀድሞው አመራር ላይ እርምጃ አለመወሰዱም ተጨማሪ ክፍተት ነው ተብሏል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከአማካሪ ድርጅት ጋር የሁለትዮሽ ውል በመግባት የ21 ግንባታዎችን ክፍያ ፈጽሟል። የዩኒቨርሲቲው ግንባታ ፕሮጀክት አስተዳደር ጽህፈት ቤት ፈጸመ የተባለው ክፍያ ዩኒቨርሲቲዎች በራሳቸው አቅም መስራት ለሚችሉት መለስተኛ ፕሮጀክቶች የግድ አማካሪ መቅጠር እንደማያ ስፈልጋቸው ከትምህርት ሚኒስቴር የወረደውን መመሪያ መሰረት በማድረግ ነው የተከናወነው፡፡ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዩኒቨርሲቲው በመመሪያው መሠረት መፈጸሙን አስታውቋል፡፡ ክፍያውን ለመፈፀም የሚያስችል ዝርዝር መረጃ ስለነበረ ለጂ አይ ዜድ ክፍያው መፈጸሙን ኃላፊዎቹ ገልፀዋል፡፡
ተሰብሳቢ ሂሳብ ለበርካታ ዓመታት የዩኒቨር ሲቲው ችግር ሆኖ መቆየቱን ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ የብዙ ዓመታት ተሰብሳቢ ሂሳብ ተንከባሎ መምጣቱን በመጠቆም ይህንንም በየመደቡ ዝርዝር አስረድተዋል፡፡ ከተሰብሳቢ ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆነው ለመምህራን የተሰጠ ብድር ነው። ከ2009 ዓ.ም የመጣው አዲሱ አመራር የሚሰጠው ብድር በመቆሙም ብድሩን እየሰበሰበ ነው። ሌሎች ተሰብሳቢ ሂሳቦችን በተመለከተ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ጋር ውይይት እየተደረገ ሲሆን፤ ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ በተወሰኑት ላይ እርምጃ መወሰድ ይጀመራል፡፡ በኃላፊዎች መቀያየር ምክንያት መፍትሄ ማግኘት ያልቻሉ መኖራቸውን በማንሳት ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ለመስጠት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡
በየዘርፉ ኮሚቴዎች በአግባቡ ተዋቅረው እቃዎቹ በናሙናው መሠረት መቅረባቸው እየተረጋገጠ ገቢ እየተደረገ ነው። ከህንፃ ምዝገባ ጋር በተያያዘ ችግር መኖሩን ገልጸዋል፡፡ ነባርና አዳዲሶቹ ህንፃዎች አለመመዝገባቸውን ጠቁመው፤ አሁን የመመዝገብ ሥራ ተጀምሯል። ንብረት ሳያስረክቡ የሚሄዱ ሠራተኞች ጉዳይ በውስጥ ድክመት የተፈጠረ ሲሆን፤ የለቀቁትን ተከታትሎ ንብረት የማስመለስ እና በህግ የመጠየቅ ድክመቶች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡
በሀገር ደረጃ ኬሚካሎችን ማስወገድ ከባድ በመሆኑም ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ ችግሩ የሚፈታበት ሁኔታ እየተጠና ነው፡፡ የጤና ጉዳት እንዳይከሰት ሰው ሊደርስበትና ብዙ ንኪኪ ሊኖር በማይችል መጋዘን ውስጥ ኬሚካሎቹ ታሽገው በጥንቃቄ እንዲቀመጡ መደረጉን አመላክተዋል፡፡
ለብልሽት የተጋለጡ በርካታ ወንበሮችን ለማስጠገን ጥረት መደረጉን፤ ሊጠገኑ የማይችሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ንብረቶችን የማስወገድ ሥራ መከናወኑን፡፡ የተበላሹ ተሽከርካሪዎች ቁጥር መቀነሱንና በጣም ከባድ ችግር ያለባቸውን ለመለየት ጥናት እየተደረገና ለማስወገድ መታቀዱን ኃላፊዎቹ አንስተዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲውን የስራ ኃላፊዎች ምላሽ ተከትሎ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ጥያቄዎችንና አስተያየ ቶችን አቅርበዋል፡፡ የተጠያቂነት ስርአት አለማ ስፈን፣ የውስጥ ቁጥጥር ስርአትን አለማ ጠናከር፣ የውስጥ ኦዲት የስራ ክፍልን በመደገፍና የሚያወጣቸውን የኦዲት ሪፖርቶች ተከትሎ እርምጃ አለመውሰድ፣ ለጂአይዜድ ለተፈጸመው ክፍያ መረጃ ካለ አለመቅረቡ፣ ለዩኒቨርሲቲው እድሳት ከመመሪያ ውጪ አላግባብ ለተከፈለው አራት ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር እርምጃ አለመወሰዱ፣ ዩኒቨርሲቲውን ከተሰብሳቢ ሂሳብ ነጻ ለማድረግ ቅድሚያ ሰጥቶ አለመሰራቱ፣ የተከማቹና የተበታተኑ ሰነዶችን በቴክኖሎጂ በመታገዝ አደራጅቶ ለመያዝ አለመታቀዱ፤ የዋና ኦዲተር ግኝትን እንደግብአት በመውሰድ ደንብና መመሪያን አክብሮ አለመሰራት ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል ናቸው፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ቃልኪዳን ፤በመርህ ደረጃ የቀጥታ ግዥ መፈፀም ባይገባም፤ በግዥ ህጉ በተቀመጠው መሠረት ግዥው አስፈላጊና አስቸኳይ ከሆነ በማኔጅመንት አስፈቅዶ ቀጥታ ግዥ መፈጸም እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በተማሪዎች መኝታ ክፍል መቃጠልና በውሃ አቅርቦት ችግር ግዥው መፈፀሙን አስረድተዋል፡፡ ከጉዳዩ አጣዳፊነት አንፃር ለመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለማሳወቅ ጊዜ ስለሚወስድ ይህን ማድረግ አልተቻለም። ክፍሉን በአዲስ መልክ ለማደራጀት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡ ለአዳራሽ ጥገና ከተፈቀደው የክፍያ ጣሪያ በላይ መከፈሉ ጥፋት ቢሆንም ገንዘቡ በአግባቡ የተከፈለ በመሆኑ እንደባከነ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። አዲሱ አመራር የኦዲት ግኝቶችን መሠረት አድርጎ እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ፤ ፈስስ የሚደረግን ገንዘብ መደበቅ፣ የትርፍ ሰዓትና የማስተባበሪያ ክፍያን ማቆም ብቻ ሳይሆን አለማስመለስ፣ ዩኒቨርሲቲው ግንባታዎችን ከመጀመሩ በፊት ቅድመ ዝግጅት አለመደረጉ ክፍተት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ክፍያዎችን ከበጀት ዓመቱ ዕቅድ ጋር አጣጥሞ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የገበያ ጥናት ሳይደረግ ለአዳራሽ ጥገና ለወጣው ገንዘብ የሚመለከተው አካል ሊጠየቅ እንደሚገባም አስጠንቅቀዋል። ለትምህርት ወደ ውጪ አገር ለሚሄዱ መምህራን የሚሠጥ ብድር ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ቢቆምም ዩኒቨርሲቲው በ2009 በጀት ዓመት ብድር መስጠቱን አቶ ገመቹ ተናግረዋል፡፡ ይህን ያደረጉና የክፍያ ሠነዶችን ያረጋገጡ ኃላፈዎችን ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ከጂ አይ ዜድ ጋር ውል የፈጸመው ትምህርት ሚኒስቴር ሆኖ ሳለ ዩኒቨርሲቲው ስራው ስለመከናወኑ የማረጋገጫ ሰነድ ሳይሟላ ክፍያ መፈጸሙ ስህተት በመሆኑም ሊታረም ይገባል ብለዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሪት ወይንሸት ገለሶ፤ የዩኒቨርሲቲው አዲስ አመራር አሰራሮችን ለመዘርጋትና ችግሮችን ለመፍታት እያደረገ ያለውን ሙከራ በማድነቅ፣ የተቀናጀ የሙስና መከላከያ ስትራቴጂ ማዘጋጀቱንም በጥንካሬ አንስተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የወሰዳቸውን እርምጃዎች ለዋና ኦዲተርና ለሚመለከታቸው አካላት በየጊዜው ማሳወቅ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
የተቀናጀ የሙስና መከላከያ ስትራቴጂውን ተግባራዊ ማድረግ፣ በኦዲት ግኝቶች ላይ እርምጃ መውሰድ፣ ከደንብና መመሪያ ውጪ ክፍያዎች እንዳይፈፀሙ፤ የተከፈሉ እንዲመለሱ ማድረግ ይገባል፡፡ በግንባታ ፕሮጀክቶች አካባቢ ያለውን አሰራር ማጥራትና ለኪራይ ሰብሳቢነት በር የሚከፍቱ ጉዳዮችን ማስተካከል፣ የውስጥ ኦዲትን ማጠናከር፣ የበጀት አጠቃቀምና ግዥን በእቅድ መምራትም አመራሩ ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸው ተመልክቷል፡፡ ተሰብሳቢ ሂሳቦችን ለይቶ እንዲመለሱ መስራት፣ ያገለገሉ ንብረቶችን በህጉ መሠረት ማስወገድ የዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች ቀጣይ የቤት ሥራዎች ናቸው፡፡

አጎናፍር ገዛኸኝ

Published in ፖለቲካ

እኤአ በ2017 ጥቅምት ወር ላይ የዓለምን ቀልብ የሳበ፣ አግራሞትን የፈጠረ፣ ድንቅ የቴክኖሎጂ ውጤት መሆኗ የተነገረላት ሶፊያ የተባለች ሮቦት ይፋ ሆነች፡፡ ሶፍያ እንደ ሰው ታወራለች፣ ጥያቄዎችን ትመልሳለች፣ ትተነብያለች፤ በቃ ሰው ሰራሽ ሰው ሆና ብቅ ብላለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ድንቅ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ውጤት ሆና ተመዝግባለች፡፡ በዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ የሳዑዲ ዐረቢያ ዜግነት ያገኘች ሮቦት ስትሆን፤ የሰውን ህይወት የተሻለ ለማድረግ በሚደረጉ ስራዎች በመሳተፍ ውጤት የማምጣት ሀሳቧ እንዳላት ተናገራለች፡፡
ዛሬ የዓለም ቴክኖሎጂ እዚህ ላይ ደርሷል፡፡ ነገ የት እንደሚደርስ መገመት አያዳግትም፡፡ ቴክኖሎጂ የኢኮኖሚ አቅም ማፈርጠሚያ በሆነበት ዘመን ቴክኖሎጂን ለመፍጠር ስርዓት መዘርጋትና ተቋም መፈጠር ቅንጦት አይሆንም፡፡ ምክንያቱም የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች በግለሰብም ሆነ በተቋማት ደረጃ ይፈልቃሉና። የእነዚህ ምርምር ውጤቶች የሚለኩት ደግሞ ወደ ተግባር ተተርጉመው የህብረተሰቡን ህይወት ማሻሻል ሲችሉ ነው።
እናም በምርምርና በፈጠራ የሚገኙ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ችግር የመፍታት አቅማቸው የሚፈተሸውም ለህብረተሰቡ ኑሮ መለወጥና ለአገር ዕድገት በሚያስገኙት ፈርጀ ብዙ ጥቅሞች ይሆናል። ስነ ህይወታዊ (ባዮቴክኖሎጂ) ሳይንስ እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቲፌሻል ኢንተለጀንስ) ወደ ተግባር ተተርጉመው ፈርጀ ብዙ ጥቅም እንዳስገኙ የበለፀጉ አገራት ተሞክሮ ያሳያል።
እነዚህ ቴክኖሎጂዎች የኢንዱስትሪና የግብርና ምርታማነትን በመጨመር፣ ጥራትን በማስጠበቅና ወጪን በመቆጠብ ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ እድገትና ለህዝብ ኑሮ መሻሻል የማይተካ ሚና እንዳላቸው የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ።
በተለይ ከግብርናው ጋር አያይዘን ብናያቸው በፍጥነት የሚያድጉ፣ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ፣ በሽታንና ተባይን የሚቋቋሙ ጣፋጭ ፍራፍሬ ያላቸውን እፅዋቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ በማባዛት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት ለማምረት የማይተካ ሚና አላቸው። እንዲሁም የግብርና ምርቶችን በጥሬ ዕቃነት የሚጠቀሙ ፋብሪካዎችንና የህዝቡን የምግብ አቅርቦት ፍላጎት ለማሟላት ወሳኝ ድርሻ ይኖራቸዋል። አዲሱን የባዮ ቴክኖሎጂ ሳይንስን ተጠቅሞ ምርታማነትን ማሳደግና ጥራት ያለው ምርት ማምረት በዓለም አቀፍ ገበያ የሚኖረውን ተወዳዳሪነት ያሳድጋል፡፡
‹‹በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርታማና በሽታን መቋቋም የሚችሉ አዋጭ አዳዲስ ዝርያዎችን በማባዛትና በማላመድ ምርታማነትን ለማሳደግ፤ እንዲሁም አገሪቱ ያላትን የብዝሀ ህይወት ሀብት ለማወቅና ለመጠቀም የሚስያችል አቅም ይፈጥራል›› የሚሉት የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዮት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ ናቸው፡፡
ዘመናዊው የባዮ-ቴክኖሎጂ ዘዴዎች ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ ህብረ-ሕዋስን ማባዛት(ቲሹ ካልቸር) ቴክኖሎጂ አንዱ ነው። ይህ ዘዴ የዕፅዋትን ነጠላ ሕዋስ በመውሰድ በቤተ-ሙከራ በተቀመመ የንጥረ ነገር ውህድ ውስጥ እንዲራባ በማድረግ የዕጽዋት ችግኞችን የማበዣ ዘዴ ነው። ቲሹ ካልቸር በተለይ ከበሽታ ነጻ የሆኑ ወይም ብዛት ያለው ምርት የሚሰጡ እፅዋቶችን በአጭር ጊዜና በከፍተኛ መጠን ማምረት የሚያስችል ዘዴ እንደሆነ ነው ዶክተር ካሳሁን የሚገልፁት።
ቡናን በቲሹ ካልቸር ዘዴ በአጭር ጊዜ በማባዛት ምርታማና ጥራቱን የጠበቀ ማድረግ እንደሚቻል ዋና ዳይሬክተሩ ለአብነት ይጠቅሳሉ፡፡ በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ቡናን በቲሹ ካልቸር ዘዴ በማባዛት ምርቱን ለመጨመርና ጥራቱን ለማስጠበቅ በተበጣጠሰ መልኩ ጥረቶች ቢደረጉም ጠብ የሚል ውጤት ሊገኝ አልቻለም ፡፡ መንግስት የቴክኖሎጂውን አስፈላጊነት በመረዳት የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን ከአንድ ዓመት በፊት አቋቁሟል፡፡ኢንስቲትዩቱም እስካሁን በተናጠል ሲካሄዱ የነበሩትን ቡናን በቲሹ ካልቸር የማባዛት ስራ በተቀናጀና ውጤት በሚያመጣ መልኩ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ከግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የግብርና ማነቆዎችን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው፡፡ በተመሳሳይ በምርት ሂደትና ክምችት ወቅት የሚከሰተውን አፍላ ቶክሲን የተባለውን ሻጋታ ኬሚካል (ፈንገስ) መከላከል የሚያስችል ቴክኖሎጂ ለመፍጠር ፕሮጀክት ተቀርጾ የምርምር ስራ መጀመሩ ተነግሯል፡፡
ዶክተር ካሳሁን በአገር ደረጃ በአሀዝ የተደገፈ መረጃ ባይኖርም በፈንገስ የተጠቃን እህል መመገብ በሰው ጤና ላይ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ስለሆነም ምርቱን ገበያ አውጥቶ መሸጥ አይቻልም፡፡ለእንስሳት መኖ ቢውልም እንኳ ይህን የተመገቡ እንስሳት በስጋውም ሆነ በወተቱ አማካኝነት ፈንገሱ ወደ ሰው ተሸጋግሮ የጤና እክል ይፈጥራል ፡፡ለዚህ አሳሳቢ ችግር መፍትሄ የሚሰጥ ቴክኖሎጂ ለመፍጠርም እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
በአፍሪካ ደረጃ ናይጄሪያ ፣ታንዛኒያና ኬንያ ቴክኖሎጂውን በምርምር አግኝተው ወደ ትግበራ መሸጋገራቸውን ዶክተር ካሳሁን ገልፀዋል፡፡ በኢትዮጵያ ግን በችግሩ ዙሪያ በቂ መረጃ ባለመኖሩ ወደ ስራ ሳይገባ ተቆይቷል፡፡ ስለዚህ የጉዳቱ መጠንና እንዴት ሊፈጠር እንደሚችል በጥናት ከተለየ በኋላ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ በመውሰድ ቴክኖሎጂውን ወደ ማመንጨት ስራ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለ10 ዓመት የምትመራበት የባዮ ቴክኖሎጂ መራሄ ድርጊት ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡
‹‹ኢንስቲትዩቱ የታለመለትን ዓላማ ለማሳካት እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ ለስራው መሰረታዊ የሆኑ ቤተ ሙከራዎችን በማደራጀት ላይ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በ10 ሚሊዮን ብር ወጪ የቤተ ሙከራ ዕቃዎችን የገዛ ሲሆን፤ ዘንድሮም ግዥ ለመፈፀም በጨረታ ሂደት ላይ ይገኛል›› የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ ይህ እስኪሟላ ድረስ የዩኒቨርሲቲዎችን ቤተ ሙከራዎች በመጠቀም ምርምርና ቴክኖሎጂ የማፍለቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ በሳይንስ ትምህርቶች የሰለጠነ የሰው ሀይል ቢኖርም የጥራት ጉዳይ አሳሳቢ ችግር ሆኗል፡፡ ችግሩን ለመፍታት ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በውጭ አገራት ‹‹በትረ ሳይንስ›› የሚል ነጻ የትምህርት ዕድል መርሀ ግብር አዘጋጅተዋል፡፡ በዚህም ከአንድ ሺ በላይ ተማሪዎች በህንድ፣በቱርክና በቻይና በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡ ይህም በቀጣይ ዕውቀትን መሰረት ያደረገ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያስችላል፡፡
ባዩ ቴክኖሎጂና ሰው ሰራሽ አስተውሎት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገትን ለማፋጠን ያስችላል፡፡ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አይሲቲ ለልማት የምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ተስፋ ተገኝ ይህን በምሳሌ ያስረዳሉ፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል አንድ የታወቀና በሙያው የተካነ ዶክተር ቢኖር፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ዕውቀቱን አገሪቱ ውስጥ ለሚገኙ ዶክተሮች በቀላሉ ማስተላለፍ ይቻላል፡፡ ይህም የህዝቡን የህክምና ወጪ ከመቀነስ ባለፈ ጤናው እንዲጠበቅ ያደርጋል፡፡
ሰው ሰራሽ አስተውሎት በዓለም ላይ ትልቅ ለውጥ እያመጣ እንደሆነ ዶክተር ተስፋ ይናገራሉ፡፡ ቴክኖሎጂው ለአገራቱ ገቢ ከማስገኝቱ ባለፈ ከኢኮኖሚ ዕድገታቸውም 20 መቶ ድርሻ አለው፡፡ በግብርና ዘርፍም የምርት ጥራትና ምርታማነትን በማሳደግ በኩል ተጨባጭ ውጤት ማሳየቱን ጠቅሰዋል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያም ለባዮቴክኖሎጂና ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ትኩረት በመስጠት እና ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የህብረተሰቡን ችግሮች ለመፍታት የሚረዳ መሰረት ለመጣል የተቀናጀ ስራ ይጠይቃል ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳንሉካን ደበበ በበኩላቸው ቴክኖሎጂዎቹ የመጪው ዘመን መወዳደሪያ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ መንግስትም ይህን ታሳቢ በማድረግ በረጅም ዕይታ ኢንስቲትዩትን ማቋቋሙን ያስረዳሉ፡፡
‹‹ሁል ጊዜ ቴክኖሎጂዎችን ምዕራባዊያን ተጠቅመውበት ሲጨርሱት እኛ ጀማሪና ተከታይ መሆን የለብንም፡፡ ቴክኖሎጂዎችን ከውጭ በመግዛትና በመቀበል በዓለም ተወዳዳሪ መሆን አዳጋች ነው፡፡ ቴክኖሎጂዎቹ የነገው ዘመን መወዳደሪያ በመሆናቸው ዛሬ መጀመር እንደሚገባ በማመን መስራት ይኖርብናል›› በማለት ከወዲሁ ቴክኖሎጂዎችን ለማመንጨት መሰረት መጣል እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡
ሰው ሰራሽ አስተውሎት የማይገባበት ዘርፍ እንደሌለ አቶ ሳንሉካን ያስረዳሉ፡፡ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ውጤት የሆነችው ሶፊያ ሮቦት ሲያናግሯት ትመልሳለች፡፡ ለምሳሌ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የት እንደሆነ ለሚጠይቃት፤ ዩኒቨርሲቲው የሚገኝበትን ቦታና ርቀቱን በኪሎ ሜትር ትናገራለች፡፡ የፌስ ቡክና የጎግል ብዙ ስርዓታቸው ከሰው ሰራሽ አስተውሎት መወሰዳቸውን አቶ ሳንሉካን ጠቁመዋል፡፡ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ኢኮኖሚን ከመደገፍና ከማቀላጠፍ ባሻገር የገቢ ምንጭም ናቸው፡፡
በኢንስቲትዩቱ የኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ማዕከል የአርቲፌሻል ቴክኖሎጂ ዳይሬክተርና ተመራማሪ አቶ ዮናስ ገብረሚካኤል ሰው ሰራሽ አስተውሎት ማሽኖችና ኮምፒተሮችን ተጠቅሞ እንደ ሰው ማሰብ፣ ማመዛዘንና መተንበይ የሚችሉ ፕሮግራሞችን የሚሰራ ስርዓት ነው ይላሉ፡፡ አሽከርካሪ አልባ መኪኖች፣ የሰብልን ጤና የሚጠቁሙ ማሽኖች የሰው ሰራሽ አስተውሎት ውጤት መሆናቸውን ለአብነት ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህ ረገድ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅና ጋና ከአፍሪካ መሰረት በመጣል ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ እንደሚገኙ ይጠቅሳሉ፡፡
ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመ ሁሉት ዓመት ባይሞላውም የሰው ሀይል ቀጥሮና የአሰራር ስርዓት ዘርግቶ ስራ ጀምሯል ይላሉ፡፡ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚሰጧቸውን አገልግሎቶችና ያሉበትን አድራሻ የሚጠቁም መተግበሪያ፣ የከተማ አውቶብሶች የደረሱበትን ቦታ፤ የመሳፈሪያ ጣቢያ ላይ በስንት ደቂቃ እንደሚደርሱ መረጃ የሚሰጡ ቴክኖሎጂዎችን በየአውቶብስ ማቆሚያዎች ለመስራት ፕሮጀክት ተቀርጾ ተግባራዊ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
እውነታው ይህ ቢሆንም ብዛት ያለው የሰው ሀይል ስራ አጥ በሆነባቸው ታዳጊ አገራት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ብዙም አስፈላጊ አለመሆኑን በመግለፅ ቴክኖሎጂውን የሚተቹ አካላት አሉ፡፡ ይህ ግን ውሃ የማይቋጥር እንደሆነ ነው አቶ ሳንሉካን የሚናገሩት፡፡ ‹‹ ሁል ጊዜ የቴክኖሎጂ ተከታይ መሆን አይገባም፡፡ ቴክኖሎጂዎቹ በባህርያቸው የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንቶች ናቸው፡፡ ዛሬ ውድድሩ በቴክኖሎጂ ፈጠራ ላይ አተኩሯል፡፡ ስለዚህ ውድድሩን ለማሸነፍ ከወዲሁ መሰረት መጣል ይገባል›› በማለት ቴክኖሎጂው በራሱ ስራ እንደሚፈጥርም አስገንዝበዋል፡፡ ቴክኖሎጂውን በመታጠቅ ለተሻለ ለውጥና ዕድገት መትጋት ይገባል፡፡

ጌትነት ምህረቴ 

Published in ኢኮኖሚ

ገና እሥራኤል እ.አ.አ በ1948 እንደ ሀገር ስትቋቋም እንደ ግብፅ፣ ሶሪያ፣ ዮርዳኖስና ኢራቅ ያሉ አገራት የሄደችበትን መንገድ ትክክል አለመሆኑን ተቃውመዋል። እሥራኤል እንደ አገር የቆመችው በፍልስጤም ምድር መሆኑን በመጥቀስ አካሄዷ አግባብነት እንደሌለው ሞግተዋል። ሆኖም በተለያዩ አገሮች ተበትነው ይኖሩ የነበሩ እሥራኤላውያን ዳግም እሥራኤልን የመመስረት ህልማቸውን እውን ከማድረግ የገታቸው ነገር አልነበረም።
ምክንያቱም በተለያዩ አገራት እንደ ጨው ተበትነው የሚኖሩት አይሁዳውያን በሰው አገር በባይተዋርነት ተገፍተዋል፣ በተለይ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ናዚ ያደረሰባቸው ግፍ መቼም ቢሆን አይረሳም፡፡ ተገድለዋል፣ ከሰብዓዊነት የራቀ ተግባር ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ቆዳቸው ተገፎና አጥንታቸው ተፈጭቶ በአሰቃቂ መልኩ ተጨፍጭፈዋል፡፡ ይህም ችግር የራሳቸውን አገር የማበጀት አስፈላጊነት እያጎላው መጣ፡፡ በተለይ በሚኖሩበት አገር መከራ የበዛባቸው አይሁዳውያን ወደ ዳግማዊቷ እሥራኤል መትመም ጀመሩ፡፡
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይም የአይሁዳውያን ቁጥር ከአጠቃላይ የፍልስጤም ምድር ነዋሪዎች 33 በመቶ ሊደርስ ችሏል፡፡ ከዚህ ሁሉ እልቂት ያለፉት አይሁዳውያን በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ እሥራኤልን እውን ማድረግ ቻሉ። በጊዜው በ40 ሺህ አይሁዶች በዚያን ጊዜዋ ፍልስጤም በመስፈር እሥራኤልን ገናና የማድረግ ጉዞ ጀመሩ። በተለያዩ ጊዜዎችም የሰፋሪዎቹ ቁጥር እያደገ መጣ፡፡ በወቅቱ ፍልስጤማውያን አይሁዳውያኑ በፍልስጤም ግዛት አገር መስርቶ መኖርን አጥብቀው ቢቃወሙትም መግታት አልቻሉም፡፡
የአይሁዳውያን ሰፈራን በግዴታ እንጂ በውዴታ እንዳልተቀበሉት መቃወም ብቻ ሳይሆን ወደ ግጭት ገቡ፡፡ ከአዲሶቹ ባለ አገሮች ጋር ደም መፋሰስ ጀመሩ። የአይሁዶችና በፍልስጤማውያን መካከል ያለው ደም መፋሰስ እስካሁን ድረሰም ሊያበቃ አልቻለም፡፡ በወቅቱ ሁኔታውን በቅርበት ሲያጤነው የቆየው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግጭቱ እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ ጣልቃ በመግባት መፍትሄ ለማበጀት ወሰነ። ድርጅቱ በጠቅላላ ጉባኤው ለግጭቱ መፍትሄነት የዛኔዋ ፍልስጤም በአይሁዶችና በአረቦች ይዞታነት ለሁለት እንድትከፈል ወሰነ፡፡ ከወራት በኋላ ነፃ የእሥራኤል መንግሥት መታወጁ የተሰማው ከዛሬ 70 ዓመት በፊት በዚህ ሳምንት ነበር።
በተለያዩ የዓለም አገራት ተበታትነው ይኖሩ የነበሩት አይሁዳውያን እንደ አገር የመቆማቸውን ዕለት ከትናንት በስቲያ አክብረውታል። ዕለቱ ፍልስጤም ወደ ሁለት የተከፈለችበት ዕለት ቢሆንም ለእሥራኤላውያን ደስታን የፈጠረ ነበር፤ በአንጻሩ በፍልስጤማውያን ዘንድ ደግሞ የኀዘንና የቁጭት ድባብን ያዘለ ዕለት ሆኗል። የቁጭቱ ደረጃ ከፍ ሲልም ዛሬም እሥራኤል የምትባል አገር እንደሌለች ተቃውሟቸውን ያሰማሉ። ከፍልስጤማውያን የተቃውሞ ጩኸት ጀርባ የአብዛኛዎቹ የአረብ አገራት ቁጣና ንዴት ጭምር የሚንጸባረቅ ነው።
በያኔዋ ፍልስጤም የእሥራኤል ነፃ መንግሥት መቋቋም ያስቆጣቸው እንደ ግብፅ፣ ሶሪያ፣ ዮርዳኖስና ኢራቅ ያሉ አገሮች እሥራኤል ነፃነቷን ሳታጣጥም ወደ ጦርነት ውስጥ ከተዋታል፡፡ ከእሥራኤል ጋር ተዋግተዋል፡፡ በዚህ ጦርነት አረቦቹ ተሸነፉ፡፡ የፍልስጤምን ልዓዋላዊነት ለማስጠበቅ ባደረጉት ጦርነት ሽንፈት ተከናንበዋል፡፡ ሆኖም ከ15 ዓመት በኋላ ዳግም እሥራኤልን ለመውጋት ጦራቸውን አደራጅተው ተመልሰዋል። አረቦችና እሥራኤል ዳግም በከፈቱት ጦርነት የእሥራኤል ክንድ አይበገሬነት በመታየቱ መጠናቀቁ ቢሰማም ከእሥራኤል ጀርባ በመሆን አሜሪካ ዳግም በእሥራኤል ምድር የድል ብስራት እንዲሰማ የማድረጓ ምስጢር አደባባይ ወጣ።
የፍልስጤምን ሉዓላዊነት ለመመለስ በእሥራኤልና በአረቦች መካከል የተካሄደው የመጨረሻው ጦርነት 44 ዓመታት አስቆጥሯል። ከዚህ ጊዜ ወዲህ ግን በአረቦች በኩል የፍልስጤምን ልዕልና በህቡዕ የማስጠበቅ እንቅስቃሴ ከጦርነት ወደ ሃሳብ መሞገት ወርዷል። የእሥራኤልን እንደ አገር የተመሰረተችበት 70ኛ ዓመት ዕለት ለእሥራኤል ሌላ ደስታ ሲፈጥር ለፍልስጤማውያን ሌላ ቁጭት ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ አሜሪካ ደግሞ አይሁዳውያን እሥራኤል የምትባል አገርን ዳግም የመሰረቱበትን 70 ኛውን ክብረ በዓል ላይ በመገኘት በመከራችሁ ከጎን እንደቆምን ሁሉ በደስታችሁም አብረን እንቆማለን የሚል ሌላ ክስተት ፈጥራለች።
በእርግጥ አሜሪካ ከመጀመሪያውኑም ቢሆን በተለያዩ የዓለም አገራት ተበታትነው ይኖሩ ከነበሩ አይሁዳውያን ጎን ቆማለች። ከዚህ ሻገር ሲል ዳግማዊት እሥራኤል በማዋለድ የአይሁዳውያንን ሃሳብ እውን እንዲሆን ድጋፍ አድርጋለች። ምን ይሄ ብቻ ከትናንት እስከ ዛሬ ድረስ የተሻገረ ድጋፍ በማድረግ እሥራኤል በኢኮኖሚም በሁለት እግሯ እንድትቆም አድርጋለች። የአሜሪካ ድጋፍ ዛሬም ቢሆን አልተቋጨም። የአገራቱ ግንኙነት ይህን መልክ ያለው መሆኑን ተከትሎ የእሥራኤል እንደ አገር የቆመችበትን ዕለት በልዩ ሁኔታ ማክበሯ የሚገርም አይሆንም። የአሜሪካ ያልተጠበቀው ክስተት ቴላቪቭ የነበረውን ኤምባሲዋን ወደ እየሩሳሌም የማዘዋወር ሥነ ሥርዓትን በዕለቱ መፈጸሟ ነው።
ኒዮርክ ታይምስ እንደዘገበው፤ የዶናልድ ትራምፕ በእሥራኤል የአሜሪካንን ኤምባሲ ቀድሞ ከነበረበት ቴል አቪቭ ወደ እየሩሳሌም የማዛወር ውሳኔ ፍልስጤማውያንን ያስቆጣ መሆኑን ዘግቧል። ፍልስጤማውያንም ምሥራቅ እየሩሳሌም የፍልስጤም ግዛት የወደፊት መቀመጫ ናት ሲሉ ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን ቀጥለዋል። በአሜሪካና በእሥራኤል መንግሥት ላይ የሚያሰሙት የተቃውሞ ወደ ግጭት አምርቶ ወትሮም ሰላም የማያውቀው ምድር ሞትን እያስተናገደ መሆኑን ዘገባው አመላክቷል።
ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው ደግሞ አሜሪካ በዕለተ ሰኞ ኤምባሲው በእየሩሳሌም መከፈቷን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በአደባባይ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ተስተውለዋል። የፍልስጤማውያን የተቃውሞ ቁጣ ከፍ ብሎ በጋዛ እና እሥራኤል ድንበር ላይ በተነሳ ግጭት የእሥራኤል ወታደሮች እርምጃ መውሰዳቸውን ጠቅሶ፤ በዚህም 52 ሰዎች ሲሞቱ 2 ሺ 400 ዎቹ ደግሞ ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲል ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር ሪፖርት የተገኘው መረጃን ዋቢ አድርጎ ዘገባው ጽፏል። ከጥይት ጨኸት ተለይቶ የማያውቀው መካከለኛው ምሥራቅ ወደ ጦርነት አውድማ የሚጓዝ መሆኑን ጽፏል። በእሥራኤልና ኢራን በኩል እንደ አዲስ ያገረሸው ውጥረት ለስጋቱ ከፍተኛውን ቦታውን የሚይዝ መሆኑ በዘገባው አካቷል።
የእሥራኤል እና ፍልስጤም የዘመናት የደም መፋሰስ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ እየሩሳሌም የእኔ ምድር ነች የሚለው የሁለቱ ወገኖች ክስ ነው። አሜሪካ ኤምባሲዋን ወደ እየሩሳሌም የማዘዋወሯ ጉዳይ ለእሥራኤል እውቅና እንደመስጠት የሚቆጠር መሆኑንም አስፍሯል። ዶናልድ ትራምፕ ወደ ነጩ ቤተመንግሥት ለመምጣት ባደረጉት የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት አሜሪካ ወደ እየሩሳሌም ኤምባሲውን የማዘዋወሩ ጉዳይ አንዱ አጀንዳቸው መሆኑን መግለጸቸው አይዘነጋም። ይሄንንም በቅርቡ አደርገዋለሁ እንዳሉት ሁሉ ቃላቸውን ተግባራዊ በማድረግ አሳይተዋል። ይሄንኑ ተከትሎም በፍልስጤም እና በእሥራኤል ድንበር አካባቢ ደም መፋሰስ የሚያስከትል ግጭት መቀስቀሱን ዘጋርዲያን ጽፏል።
ሲኤን ኤን እንደዘገበው፣ አሜሪካ በእሥራኤል የሚገኘውን ኤምባሲዋን ወደ እየሩሳሌም ማዘዋወሯ ተገቢ እንዳልሆነ የእስላማዊ አገራት ጥምረት ተቃውሞውን አሰምቷል። አገራቱ በጥምረት ባወጡት መግለጫ አሜሪካ እየሩሳሌም የእሥራኤል መዲና ናት ማለቷ እርባና ቢስ ነው። የአሜሪካ ውሳኔ በፍልስጤምና እሥራኤል መካከል ስትጫወት ከነበረው የዳኝነት ሚና ጋር የሚጣረስና ከዚህ በኋላም ሊሆን የማይችል ነው። ከዚህም በተጓዳኝ በቀጣናው ያለውን ውጥረት በይበልጥ እንዲባባስ የሚያደርግ ነው ሲሉ ድርጊቷን ኮንነውታል።
ዘገባው እንደሚለው፤ የፍልስጤሙ መሪ ማሕሙድ አባስ በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት በጉዳዩ ጣልቃ መግባት እንዳለበት ቀድሞውኑም እንደሚወተውቱት ሁሉ አሁንም ዳግመኛ የተባበሩት መንግሥታት ጣልቃ ገብቶ መፍትሄ እንዲያበጅ ጥሪያቸውን አቅርበዋል። «አሜሪካ ሆን ብላ የእሥራኤል-ፍልስጤም የሰላም ሂደትን ፉርሽ የሚያደርግ ድርጊት ከመፈፀሟም በላይ ለፅንፈኝነትና ሽብርተኝነት መንገድ እየከፈተችም ነው» ሲሉ አባስ መግለጻቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ዋሽንግተን በወሰነችው ውሳኔ ምክንያት ለሚደርሱ ጥፋቶች ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ መሆኗ እንደማይቀርም ከጥምረቱ በኩል እየተነገረ መሆኑን አያይዞ ጽፏል።
ቢቢሲ በሌላ ዘገባው፤ የኤምባሲውን መዛወር ተከትሎ የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ቅሬታ አሰምቷል። በእሥራኤል የሚገኙ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደሮች በዝግጅቱ ላይ ባለመገኘት ተቃውሟ ቸውን ያሰሙ ሲሆን፤ በተለየ ሁኔታ ደግሞ ቱርክ የአሜሪካንን ተግባር ክፉኛ በመኮነን ግንባር ቀደም መሆኗን ዘግቧል። በጋዛ እና እሥራኤል ድንበር በእሥራኤል ወታደሮች እየተገደሉ ያሉት ፍልስጤማውያን ጉዳይ ክፉኛ እንደሚያሳስባት ቱርክ ማስታወቋን ጽፏል።
እየሩሳሌም ሙስሊሞች እንደ 3ኛ ቅዱስ ቦታቸው የሚቆጥሩት የአል አቅሷ መስጊድ የሚገኝ ሲሆን፣ በሌላ በኩል አይሁዶችም የ3ሺህ ዓመት ታሪክ ያለው ቅዱስ ስፍራቸው አድርገው በመቁጠራቸው ግጭቱ የከፋ እንዲሆን አድርጎታል። ሁኔታውም በዚህ መልኩ የመቀጠሉ ሃቅ፤ የፍልስጤማውያን እና እሥራኤልን ደም የማፋሰስ ሁኔታ ዳግም የሚያድሰው ይሆናል።
በዓለም አገራት ላይ በቀጥታም ይሁን በእጅ አዙር የተፅዕኖ ብትሯን በማሳረፍ ተሰሚ ለሆነችው አሜሪካ ሌላው ጦስ እንደሚሆን ተተንብዮአል። የአውሮፓ ኅብረት የአሜሪካን ውሳኔ ቅር መሰኘቱ የአሜሪካን የተሰሚነት እና የኃያልነቷ ግስጋሴ መክሸፍ ምልክት እንደሚሆን ዘገባው አስፍሯል። የተባበሩት መንግሥታት የውሳኔ ሃሳብንም ከዚሁ ጋር ተያይዞ ያለው ቅቡልነት ከአሜሪካ የኃይል ጥላ ስር የማይወጣ እንደሆነ የትናንት በስቲያው ጉባኤ አመላካች እንደሆነ የዓለም መገናኛ ብዙኃን በተለያየ ሁኔታ ዘግበዋል፡፡

 ዳንኤል ዘነበ

Published in ዓለም አቀፍ
Wednesday, 16 May 2018 17:22

የመድኃኒት ያለህ

ከዓመት በፊት ነው፡፡ አንዲት የካንሰር ህመምተኛ ወይዘሮ በካንሰር የተጎዳውን የሰውነት አካባቢ በጨረር የማቃጠል (የኬሞቴራፕ) ህክምና ታዞላት ትከታተላለች፡፡ ይህ ህክምና በተለይም በመጀመሪያዎቹ ቀናት በጣም ከባድ ነው፡፡ ህመምተኞቹ ህክምናውን ሲጀምሩ ከባድ ስቃይን ለማሳለፍ ይገደዳሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ደግሞ ኬሞቴራፒ ሌላ የጤና እክል የሚያስከትል የጎንዮሽ ጉዳት አለው፡፡ ግን ያለው አማራጭ ይኸው በመሆኑ ህክምናውን መውሰድ ግድ ነው፡፡
የካንሰር ታማሚዋ ወይዘሮም ህክምናውን እየተከታተለች ሳለ ህመሙ ይፀናባታል፡፡ ምግብ መውሰድ በማቆሟ ግሉኮስ እንድትጠቀም ተደረገ፡፡ ይህም የሚፈለገውን ውጤት ሊያመጣ አልቻለም፡፡ ወይዘሮዋ አቅሟ እየተዳከመ የመኖር ህልውና ጥያቄ ምልክት ውስጥ ወደቀ፡፡ በዚህን ጊዜ ሃኪሞቹ አማራጭ ያሉትን ሃሳብ አቀረቡ፡፡ የወይዘሮዋ ሰውነትን ለማጠናከርና በሽታውን የመቋቋም አቅሟን ለመጨመር የሚረዳ ሌላ ግሉኮስ እንድትወስድ አዘዙላት፡፡
የታዘዘውን መድሃኒት ለማግኘት ታዲያ እጅግ አስቸጋሪ እንደነበር ታሪኩን ያወጋኝ ጓደኛዬ ነግሮኛል፡፡ የወይዘሮዋ ቤተሰቦች በየመድሃኒት ቤቶች ቢንከራተቱም መድሃኒቱን ሊያገኙት አልቻሉም፡፡ የቤተሰባቸውን አባል ለመታደግ ያደረጉት ሩጫ በሚፈለገው ጊዜ ሊደርስ አልቻለም፡፡ በዚህም ሳቢያ ወይዘሮዋ እስከ ወዲያኛው ለማንቀላፋት ተገዳለች፡፡
ደረጃውና ህመሙ ቢለያይም የመድሃኒት እጦት (መጥፋት) ብዙዎችን ለከፍተኛ እንግልትና ስቃይ ዳርጓል፡፡ ለህመማቸው መፍትሔ ፍለጋ ወደ ጤና ተቋማት አምርተው፣ ህክምናውን አግኝተው፣ የታዘዘላቸውን መድኃኒት በማጣት የሚሰቃዩ ቤት ይቁጠራቸው፡፡ በፈታኝ ውጣ ውረድ የሕክምና ማዕከላት ሄደው የታከሙ ሰዎች ለህመማቸው ማስታገሻና መፈወሻ መድኃኒት ካላገኙ መታከማቸው ትርጉም አልባ ነው፡፡ በሕይወትና በሞት መካከል ሆነው ለሚያጣጥሩ ህሙማን ደግሞ የመድኃኒት መጥፋት ትልቅ አደጋ ነው፡፡
የመድኃኒቶች እጥረት ዜጎችን ለእንግልትና ስቃይ ከመዳረጉ በተጨማሪ ጥራታቸውና ጤንነታቸውን ያልጠበቁ፣ ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች ለገበያ እንዲቀርቡ በር ይከፍታል፡፡ ይህ ደግሞ ከህመሙ መዳንን ለሚሻ ዜጋ ሞቱን ከማፋጠን ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ጊዜ ባለፈባቸው መድኃኒቶች ብዙዎች እስከ ወዲያኛው ማሸለባቸው ፀሃይ የሞቀው ሃቅ ነው፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት የመድኃኒት እጥረት ትልቁ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በተለይም ከበሽታዎቹ ባህርይ አንፃር በየጊዜው ሊወሰዱ ግድ የሆኑ የስኳር በሽታ ዓይነት መድኃኒቶች (ኢንሱሊን) ከገበያ ላይ ጠፍተው ነበር፡፡ በዚህም በርካቶች ለስጋትና ድንጋጤ ተዳርገዋል፡፡ የልብና የአስም መድሃኒቶችም ከገበያው ተሰውረው በመቆየት ዜጎችን ማንገላታቸው አይረሳም፡፡ ከተለመደው ሂሳብ በላይ የገዙና ውጭ አገር የሚኖሩ ዘመዶች እንዲልኩላቸው የእርዳታ ድምፃቸውን ያሰሙም ጥቂት አይደሉም፡፡ ህመማቸውን ከማስታገስ ይልቅ ቁጭ ብለው መማረርና ማልቀስን ሥራቸው ያደረጉ በርካታ ናቸው፡፡ የመድሃኒት መጥፋት ብዙዎችን አንገላቷል፤አሰቃይቷል፡፡
ህብረተሰቡ መድሃኒቶችን በገበያ ላይ ባለማግኘቱ እሮሮ ከማሰማት አልፎ ተስፋ ወደ መቁረጥ ደረጃ ደርሷል፡፡ ‹‹አትመመኝ አይባልም…›› እንደሚባለው ሰው ፈልጎና ፈቅዶ አይታመምም፡፡ በሽታ በአጋጣሚ ይከሰታል፡፡ ይህን የጤና ጠንቅ ለመከላከልና ለማስወገድ ቀዳሚው እርምጃ ወደ ህክምና ተቋም መሄድ ነው፡፡ ባለሙያው ተገቢውን ምርመራ አድርጎ ለታማሚው መድኃኒት ያዛል፡፡ ህመምተኛውም የታዘዘለትን መድኃኒት ለመግዛት ወደ መድሃኒት ቤት ያመራል፡፡ እዛ ደርሶ ‹‹መድኃኒቱ የለም››ሲባል ግን ህመሙ ይብስበታል፤ተስፋ ይቆርጣል፡፡
አጋጣሚውን በመጠቀም ኪሳቸውን ለመሙላት የሚጥሩ አንዳንድ ሙያዊ ሥነ ምግባር የጎደላቸውና ህሊናዊ ዳኝነትን የረሱ ግለሰቦች መኖራቸው ደግሞ እጅጉን ያሳዝናል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች መድሃኒቶቹ ቀደም ሲል ሲሸጡ ከነበሩበት ዋጋ በእጥፍ አሳድገው ሲቸረችሩ ተስተውሏል፡፡ የሚገርመው ደግሞ የዋጋ ጭማሪው ጠፉ በተባሉት መድኃኒቶች ላይ ብቻ አለመወሰኑ ነው፡፡ ህገ ወጥ ጥቅም ፈላጊዎቹ ‹‹የመድኃኒት ዋጋ ጨምሯል›› በሚል የፈጠራ ምክንያት ዋጋ እየቆለሉ ይሸጣሉ፡፡ የታመመ አማራጭ የለውምና በተባለው ዋጋ ገዝቶ ይሄዳል፡፡ እነዚህ ህሊናቸውን ያሳወሩ ግለሰቦች በህዝቡ ህመም ኪሳቸውን ለመሙላት ይሯሯጣሉ፡፡ መድኃኒቶችን ደብቀው ‹‹የለም›› በማለት በህሙማን ህይወት ላይ ይቆምራሉ፡፡
ሌሎች ስግብግቦችና ግዴለሾች ደግሞ ጊዜ ያለፈባቸውን መድኃኒቶች ለተጠቃሚዎች በማቅረብ በወንጀል የተጠቀለለ ገንዘብ ለመሰብሰብ ይሯሯጣሉ፡፡ ሞትን የሚያፋጥኑ መድኃኒቶችን በመሸጥ ካዝናቸውን ይሞላሉ፡፡ የዜጎች መሰቃየትና መሞት ምናቸውም አይደለም፡፡ የመድኃኒቱ ገቢ ማምጣት እንጂ የአገልግሎት ጊዜው ማለፍ አያሳስባቸውም፡፡
የመድሃኒት እጥረት መባባስን ተከትሎ የፌዴራሉ የመድኃኒት አቅርቦት ፈንድ ኤጀንሲ ችግሩ የማስፈፀም አቅም ማነስ መሆኑን ሲናገር ተሰምቷል፡፡ ሆስፒታሎች፣ የከነማ መድሃኒት ቤቶች፣ ጤና ተቋማት በዓመት አራት ጊዜ የመድሃኒት ግዥ መፈፀም ቢኖርባቸውም ይህን አለማድረጋቸው ለእጥረቱ ምክንያት እንደሆነ አስታውቋል፡፡ የተደራሽነት ችግርም ሌላው ምክንያት ነው ተብሏል፡፡
ይህን ለመፍታትም ኤጀንሲው መፍትሔ ያለውን አማራጭ ወስዷል፡፡ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጋር ስምምነት በመፈራረም መድኃኒቶችን በቀይ መስቀል መድኃኒት ቤቶች በኩል ለተጠቃሚዎች ለማድረስ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡ በመሆኑም ቀይ መስቀል ከኤጀንሲው መድሃኒቶችን በብድር በመውሰድ ለገበያ ያቀርባል፡፡ ከኤጀንሲው የሚረከባቸውን መድሃኒቶችም በስር ባሉ 40 መድኃኒት ቤቶች ለህብረተሰቡ ያሰራጫል፡፡
የአገር ውስጥ የመድኃኒት አምራቾች የአቅም ውስንነትም ለመድኃኒት እጥረት እንደ አንድ ምክንያት ሲጠቀስ ተሰምቷል፡፡ አምራቾች የሚፈለገውን መድኃኒት በብዛት የማቅረብ የአቅም ውስንነት እንዳለባቸው ቢገለፅም፤ እነሱ በበኩላቸው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ትልቅ ፈተና እንደሆነባቸው ነው የተናገሩት፡፡ ይህም መድኃኒቶችን ከአገር ውስጥ ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት መፈታተኑ አይካድም፡፡
በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የአገሪቱ የጤና ወጪ 33 በመቶ በዜጎች፣ 33 በመቶ በመንግስት 34 በመቶ በዕርዳታ እንደሚሸፈን ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከ2007 ዓ.ም እስከ 2010 ዓ.ም አጋማሽ ኢትዮጵያ 36 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው መድሃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎችን ከለጋሾች በመቀበል ጥቅም ላይ አውላለች። መንግስት የመድኃኒት እጥረትን ለመከላከል 20 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ በመመደብ በኤጀንሲው በኩል ግዥ ያከናውናል፡፡
መረጃዎች ይህን ቢያመላክቱም አሁንም ታዲያ የመድኃኒት አቅርቦትና ፍላጎት አልተጣጣመም፡፡ ህብረተሰቡ በመድኃኒት ቤቶች፣ ጤና ተቋማትና ሆስፒታሎች የሚፈልገውን መድኃኒት፤ በሚፈልገው ጊዜና መጠን እያገኘ አይደለም፡፡ ትላልቅ የሚባሉ የመንግስት ሆስፒታሎችና መድኃኒት ቤቶች በመድኃኒት ምች ተመትተው ሰንብተዋል፡፡
18ሺ የጤና ኬላዎች፣ አራት ሺ ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች እንዳሏት የሚነገርላት ኢትዮጵያ የህክምና ተቋማቱ አስፈላጊዎቹን መድኃኒት ካልያዙ አገልግሎታቸው ከግማሽ አይዘልም፡፡ ህመምተኞች በህክምና ተቋማት ከምርመራ በተጨማሪ መድኃኒት ያስፈልጋቸዋልና፡፡ ተቋማቱ ይህን ማሟላት ካልቻሉ ተልዕኮዋቸው ከማማከር የዘለለ ውጤት አይኖረውም፡፡ ህመምተኛው በሽታውን አውቆ ተገቢውን መድኃኒት ካልወሰደ ውጤቱ ባዶ ነው የሚሆነው፡፡ እናም የህክምና ተቋማት ለምርመራና ከምርመራ በኋላ የሚሰጡ መድኃኒቶችን አሟልተው መገኘት አለባቸው፡፡
ይህን ችግር የመፍታቱ ጥረት በደንብ ሊጠናከር ይገባል፡፡ ጉዳዩ የአንድን አካል ጥረት ሳይሆን የብዙዎችን የተባበረ ክንድ ይፈልጋል፡፡ መድኃኒት ቤቶች፣ አምራቾች፣ አቅራቢዎችና አከፋፋዮች የድርሻቸውን ሊወጡ ግድ ይላል፡፡ መድኃኒትን በመግዛት የሚያቀርበው መንግስታዊው የመድኃኒት አቅርቦት ፈንድ ኤጄንሲ ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡ የእጥረቶችን መንስዔ በማጣራት ለመፍትሔ መትጋት ይጠበቅበታል፡፡ ወቅታዊ የመድኃኒት ፍላጎትን መሰረት ያደረገ አቅርቦት እንዲኖር መስራት አለበት፡፡
መድኃኒት ቤቶች የሙያውን ሥነ መግባር ጠብቀውና ህጉን አክብረው መድኃኒቶችን ለተጠቃሚዎች ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ መድኃኒቶችን በመከዘን በሰው ህይወት ላይ በመቆመር የተሻለ ገንዘብ ፍለጋ የሚማትሩ አንዳንድ ግለሰቦችም ከህገ ወጥ ድርጊታቸው መታቀብ አለባቸው፡፡ የጥራት ደረጃውን የጠበቀና ጤናማነቱ የተረጋገጠ መድኃኒት በፍትሃዊ ዋጋ በማቅረብ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ግድ ይላል፡፡ የአገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች አቅማቸውን በማጠናከር የመድኃኒት እጥረት እንዳያጋጥም የቤት ሥራቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ ‹‹የመድሃኒት ያለህ›› ለሚለው ዜጋ መድረስ አለባቸው፡፡ በሂደቱም መድኃኒቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት የተያዘውን ዕቅድ ያሳካሉ፡፡
ለመድኃኒት እጥረት ምክንያት የሆኑትን ጉዳዮች በመለየትና በመፈተሽ አፋጣኝና ዘላቂ መፍትሔዎችን ማስቀመጥ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶች በማረምና ጉድለቱን በመሙላት በቂና የጥራት ደረጃውን የጠበቀ መድኃኒት ለተጠቃሚዎች ለማድረስ መስራት ይገባል፡፡ በ‹‹መድኃኒት ያለህ›› የሚሰቃየውን ዜጋ ፍላጎት ለማረጋገጥ ትግሉ መፋፋም ይኖርበታል፡፡ በተለይም መድኃኒትን በመከዘን በሰው ሰራሽ ምክንያት እጥረት እንዲፈጠር በሚያደርጉ አካላት ላይ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር በደንብ መጠናከር አለበት፡፡ ለዚህ የሚረዳ ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡

ሠላም ዘአማን

Published in አጀንዳ

በፌዴራሉ ዋና ኦዲተር በተደጋጋሚ ስህተት መፈፀማቸው ከሚነገርላቸው ተቋማት ዩኒቨርሲቲዎች ቀዳሚውን ቦታ ይይዛሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቹ በሀብት አጠቃቀም፣ በህግ አተገባበር እንዲሁም ግልፅነትና ተጠያቂነትን የተላበሰ አሰራር በመዘርጋት ረገድ ሰፊ ክፍተት እንዳለባቸው ዋና ኦዲተር በተከታታይ የኦዲት ግኝት ሪፖርት ያቀርባል፡፡
በአንድ ወቅት ዋና ኦዲተር የዩኒቨርሲቲዎችን የአሰራር ክፍተት ሪፖርት ሲያቀርብ ከአንድ የምክር ቤት አባል‹‹ ዩኒቨርሲቲዎቹ አውቀው ነው እንዴ የሚያጠፉት?›› እስከ ማለት የደረሰ አስተያየት ተሰንዝሯል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቹ ለሌሎቹ ተቋማት አርዓያ መሆን ሲገባቸው በስህተት ጎዳና ላይ መራመዳቸው ‹‹ነገሩ እንዴት ነው?›› ማስባሉ አልቀረም፡፡
በየተቋማቱ የሚመደብ ባለሙያና አመራር ከእነዚህ የትምህርት ተቋማት የሚወጣ መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ ጉዳዩ ልዩ ትኩረት እንደሚሻ ያሳያል፡፡ በአሰራር ክፍተት በተደጋጋሚ ስማቸው ጎልቶ ከሚጠቀሱ ዩኒቨርሲቲዎች ከሚወጡ ባለሙያዎችና አመራሮች የተሻለ ነገር መጠበቅ አስቸጋሪ ማድረጉም አልቀረም፡፡
በቅርቡ እንኳን የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር መቀሌና ዲላ ዩኒቨርሲቲዎች ከህገ ወጥ ክፍያና ግዥ ፣ ከገቢ አሰባሰብ፣ ከንብረት ምዝገባና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ጉድለቶች እንዳለባቸው በኦዲት ግኝት ማረጋገጡን በመጠቆም የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ሪፖርቱን ለምክር ቤት አቅርቧል፡፡ እነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ለማሳያነት ቀረቡ እንጂ ችግሩ በሌሎቹም በስፋት ይስተዋላል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎቻችን ሁሌም ከችግር ፀድተው ለመታየት አልበቁም፡፡ የዚህ ዋናው ችግር ደግሞ ኃላፊነትን በአግባቡ ካለመወጣት ይመነጫል፡፡ የዩኒቨርሲቲው አመራር ኃላፊነቱን በብቃትና በጥራት አለመወጣቱ ለብልሹ አሰራር በር ይከፍታል፡፡ የሥራ አፈፃፀሞችን በመገምገም ድክመትና ጥንካሬን ከመፈተሽ ይልቅ ለስህተቱ ምክንያት ፍለጋ እጁን ወደ ሌሎች ሲቀስርም ይስተዋላል፡፡ ይህ ደግሞ ለውጥም፣ ውጤትም አያመጣም፡፡
የዕውቀትና የአቅም ግንባታ ማዕከል የሆኑት ዩኒቨርሲቲዎች ከአቅም በታች አፈፃፀም ማስመዝገባቸው ከቆሙበት ተልዕኮ ጋር የሚቃረን ዕውነታ ነው፡፡ ተገቢውን ዕውቀትና ክህሎት የጨበጠ እና በመልካም ሥነ ምግባር የታነፀ ዜጋን ለማፍራት የሚጥር ዩኒቨርሲቲ የችግር ማሳያ ሆኖ መቅረብ የለበትም፡፡ ለችግሮች የተለያዩ መፍትሔዎችን ማፍለቅ የሚችሉ ባለሙያዎችን የሚያፈሩ ተቋማት በባለሙያ እጥረት ለስህተት መዳረጋቸውን በምክንያትነት ማቅረብ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡
መስተካከል የሚገባውን በማስተካከል፤ ጥሩ ውጤት የተመዘገበበትን በማጠናከር መሄድ ይገባል፡፡ ችግር በታየባቸው አካላት ላይም ህጋዊውን ሥርዓት ተከትሎ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ ተገቢነቱ አያጠያይቅም፡፡ ለዚህ ደግሞ የሁሉም ድርሻና ርብርብ ወሳኝ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቹ ራሳቸውን በመፈተሽና በመገምገም ሥራዎች ህጋዊውን ሥርዓት ተከትለው እንዲከናወኑ መትጋት አለባቸው፡፡ ስህተቶች ሲኖሩም ሳይውሉና ሳያድሩ መፍትሄ እንዲያገኙ መጣር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዋናው ኦዲተርም በዩኒቨርሲቲዎች ላይ የሚያገኛቸው የኦዲት ግኝቶች መስተካከላቸውን በየጊዜው እየተከታተለ ለሚመለከተው አካል ማቅረብ ይኖርበታል፡፡
በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ባለሙያዎች ለሚፈጽሙት ችግር የበኩላቸውን ድርሻ መውሰድ አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓቱን ግልፅና ጠንካራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የትምህርት ተቋማቱ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሳይወጡ ሲቀር ተገቢውን እርምጃ መውሰድ ይገባል፡፡ አሁን ላይ የሚታየው ግን ከጠንካራ እርምጃ ይልቅ ማስታመምን ትኩረት ያደረገው አካሄድ መስተካከል ይኖርበታል፡፡ በማሳሰቢያዎችና ማስጠንቀቂያዎች ለውጥና መሻሻል ካልታየ ቀጣዩን ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ ይገባል፡፡
ይህን አለማድረግ አመራሮች ተጠያቂነትን ሳይፈሩ እንዳሻቸው እንዲንቀሳቀሱ ያበረታታል፡፡ አጥፊ ካልተጠየቀ በሌላው ዘንድ ‹‹የምን ይመጣል?›› እብሪት ይነግሳል፡፡ ስህተትን ዝም ብሎ የማየት አመለካከት ጉልበቱን አበርትቶ ‹‹በምን አገባኝ›› ጎዳና ተመላላሹ ይበዛል፡፡ ስለ እውነት የሚታገሉ ሰዎችንም ሞራል ይነካል፡፡ ብልሹ አሰራርና ማን አለብኝነት ይበረታል፡፡ የህዝብና የአገር ሀብት ከታሰበለት ዓላማ ውጭ ይውላል፤ይባክናል፡፡
ይህን መስመር በማስያዙ ሂደት የትምህርት ተቋማቱን በበላይነት የሚከታተለው ትምህርት ሚኒስቴር ትልቅ ድርሻ አለበት፡፡ ችግሮችን በየጊዜው ከሥር ከሥር የመፍታትን ልምዶች ማጠናከር ይኖርበታል፡፡ የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓቱን ማዘመንም ይጠበቅበታል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ አለባቸው፡፡ የትምህርት ማዕከላት የመልካም ሥራ እንጂ የችግር ማሳያዎች እንዳይሆኑ መስራት ይገባል፡፡ በህዝብና በአገር ሀብት ላይ ለሚደርሰው ብክነትና ጥፋት የሚመለከታቸውን አካላት በህግ አግባብ የመጠየቁ እርምጃም ከማስጠንቀቂያ ያለፈ መሆን አለበት፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።