Items filtered by date: Wednesday, 02 May 2018

በዓለማችን ተወዳጅነትን ካገኙ ስፖርቶች አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት መጀመሩን የታሪክ መረጃዎች ያስረዳሉ። ከ200 ባላነሱ አገራትም ይዘወተራል-የቴኳንዶ ስፖርት፡፡ ውልደቱን ከወደ ኮሪያ ማድረጉ የሚነገርለት ቴክኳንዶ በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት ተቀባይነት በማግኘት መዘውተር የጀመረው ግን ከ20 ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ መሆኑን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ በተለይም እአአ በ1955 ዓ.ም ከፍተኛ ተቀባይነት በማግኘቱ ስፖርቱ ለመስፋፋት ችሏል፡፡
የዓለም አቀፍ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን መስራች ኮሪያዊው ጄነራል ቾይ ሆንግ ሂ ጥበቡን ለዓለም በማስተዋወቅ ስማቸው ጎልቶ ይነሳል፡፡ ‹‹የቴኳንዶ ፈጣሪ›› የሚል ማዕረግ እስከ መጎናጸፍ የደረሱት እኝህ ሰው የቴክኳንዶ ስፖርት ብዙ ተከታዮች እንዲኖሩት ማስቻላቸውም ይነገራል፡፡ በአሁኑ ወቅት ቴክኳንዶ በዓለም ላይ ከ50 ሚሊዮን በላይ ስፖርት ተከታዮች እንዳሉት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ኢትዮጵያና ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ
ከስፖርታዊ እንቅስቃሴነት በዘለለ በተለያዩ አገራት በወታደራዊ የስልጠና ማዕከላት እንደ አንድ ስልጠና የሚሰጠው ቴክኳንዶ በኢትዮጵያ መቼ እንደተጀመረ በትክክል የተፃፈ መረጃ የለም፡፡ ሆኖም ግን በ2009 ዓ.ም ‹‹የኢንተርናሽናል ቴኳንዶ መማርያ›› በሚል ርዕስ በኢንተርናሽናል ማስተር ኪሮስ ገብረመስቀል የታተመው መጽሃፍ ስፖርቱ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ያትታል፡፡
ቴክኳንዶ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ከአምስት አስርት ዓመታት ያላነሰ ዕድሜ እንዳስቆጠረ መላ ምቶች ቢኖሩም ህዝባዊነትን በመላበስ ተወዳጅ መሆን የቻለው ግን ደርግ ወደ ስልጣን ከመጣ ከአስር ዓመት በኋላ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በ1976 ዓ.ም የደርግ መንግስት የፖሊስ ሠራዊትን ለማጠናከር ቴኳንዶ በስፋት መዘውተሩ በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡ ከወታደራዊ ሥልጠና ውጭ ግን ስፖርቱን መለማመድ የተከለከለ ነበር፡፡
ክልከላውን ተላልፎ ሲለማመድ አልያም እንቅስቃሴ ሲያደርግ የተገኘ ሰው ዕጣ ፈንታው እስከ መታሰር የሚደርስ እርምጃን መቀበል ነው፡፡ የቴኳንዶ ስፖርት ከተከለለበት አጥር በመውጣት ህዝባዊ በሆነ መልኩ የትኛውም ዜጋ መሠልጠን የጀመረው ከ1980ዎቹ በኋላ እንደሆነ መፅሃፉ ያስረዳል።
የቴኳንዶ ዕድገት ተግዳሮቶች
የአዲስ አበባ ቴክኳንዶ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ቴክኳንዶ አሶሴሽን የቦርድ አባልና የዳኞች ሊቀመንበር ኢንተርናሽናል ኢንስትራክተር ኤልያስ ኩመል፤ የቴኳንዶ ስፖርት በኢትዮጵያ በይፋ እንቅስቃሴው የተጀመረው በ1985 ዓ.ም መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ ከሠላሳና አርባ ዓመታት በላይ ለስፖርቱ ብዙ መስዋዕትነት መከፈሉን ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹ከኛ በፊት የነበሩት አስተማሪዎቻችን ብዙ ፈተናዎችን አሳልፈው ስፖርቱን ለዚህ አብቅተዋል›› በማለት።
ኢንስትራክተር ኤልያስ እንደሚሉት፤ በጊዜው የነበረው ሥርዓት ቴክኳንዶን ለመስራት አይፈቅድም፡፡ ተደብቆ ለመስራት የሚደረገው ጥረትም አስቸጋሪ ነበር፡፡ በቀደሙት ጊዜያት እንደ ሳሙኤል ወጋየው፣ ሳሙኤል ነጋሽና ሌሎች በስፖርቱ ያለፉት ባለሙያዎች ከባድ ችግርን ተጋፍጠዋል፡፡ በህዝቡ ዘንድ የነበረው ተቀባይነትም እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ እነሱ በከፈሉት መስዋዕትነት ቴኳንዶ የዛሬውን ገፅታ ለመላበስ ችሏል፡፡
የኢንተርናሽናል ማስተር ኪሮስ ገብረ መስቀል መፅሃፍም ህዝቡ ስለ ስፖርቱ የነበረው አመለካከት በጣም ዝቅተኛ ስለነበር ቴኳንዶን ለማስፋፋት አስቸጋሪ እንደነበር ይገልፃል፡፡ ይህና የማሰልጠኛ አዳራሽ አለማግኘት ስፖርቱ በሚፈለገው ደረጃ እንዳያድግ እንቅፋት ሆኗል፡፡
እስከ 90 ዎቹ አጋማሽ የስፖርቱ እንቅስቃሴ በፈተና የተሞላ እንደነበር ነው የሚነገረው፡፡ ከ1995 ዓ.ም በኋላ ያለው ጉዞ ግን ቀደም ሲል በቴኳንዶ ላይ የተጋረጡት ፈተናዎች እየቀነሱ፣ስፖርቱ እያደገ የመጣበት ጊዜ ነው፡፡ ይህም ቴኳንዶ ወደ ስኬት የመጣበት ጊዜ እንደሆነ ተመልክቷል።
ቴኳንዶን ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት በተወሰኑ ግለሰቦች ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ ለበርካታ ዓመታት መጓዙን ኢንስትራክተር ኤልያስ ይናገራሉ፡፡ ህብረተሰቡ ለስፖርቱ ያለው ግንዛቤ እየተሻሻለ መምጣቱ ስፖርቱ እያደገ እንዲመጣ አድርጓል፡፡ በአገሪቱ ያሉ ባለሙያዎችም ወደ ውጭ አገር እየሄዱ ስልጠናዎችን የመውሰድ ዕድል አገኙ፡፡ የውጭ አገር ስልጠና ዕድሉ በዘርፉ ተገቢውን ዕውቀትና ክህሎት የጨበጡ አሰልጣኞችን በብዛት ለማግኘት ረድቷል፡፡ ስፖርቱ ወደ ፊት እንዲራመድም ትልቅ አስተዋፅዖ ማበርከቱን ኢንስትራክተር ኤልያስ ያስረዳሉ፡፡
ይህን ተከትሎ ስፖርቱ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተስፋፋ መጣ። የተለያዩ ክለቦች መመስረታቸውም ለስፖርቱ ማደግ የበኩላቸውን አስተዋፅዖ አበረከቱ፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ በኢትዮጵያ ቴኳንዶ ማህበር የታቀፉ ከ110 በላይ ህጋዊ እውቅና የተሰጣቸው ክለቦች አሉ፡፡ ከ15ሺ በላይ በሆኑ ስፖርተኞችም ይዘወተራል። ይህም ስፖርቱ ካለፉት ጊዜያት አንፃር በከፍተኛ ደረጃ እያደገና ሰፊ ተቀባይነትን እያገኘ መምጣቱን ያሳያል ይላሉ-ኢንስትራክተር ኤልያስ፡፡
በማህበራት ላይ የተንጠለጠለ ጉዞ
ለስፖርቱ እዚህ መድረስ በሶስት ግለሰቦች የተቋቋሙ ማህበራት ሚና ጉልህ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ የኢትዮጵያ ቴኳንዶ አሶሴሽን፣ ኢትዮ ዩናይትድ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ አሶሴሽን እና የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ አሶሴሽን የቴኳንዶ ስፖርት በኢትዮጵያ እንዲስፋፋና እንዲያድግ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡
እነዚህ ማህበራት በአንድነት የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ፌዴሬሽን በመፍጠር ስፖርቱ በክልሎች እንዲስፋፋ አድርገዋል፡፡ በሂደትም በርካታ የቴኳንዶ ስፖርት አዘውታሪዎችን ለማፍራት ችለዋል፡፡
ኢንተርናሽናል ኢንስትራክተር አብዲሳ ረጋሳ በበኩላቸው መገናኛ ብዙኃን ለስፖርቱ አነስተኛ ትኩረት መስጠታቸው ስፖርቱ በሚፈለገው ደረጃ እንዳያድግ የበኩሉን አስተዋፅዖ አበርክቷል ይላሉ፡፡ መገናኛ ብዙኃኑ እንደ ሌሎቹ የስፖርት አይነቶች ለቴኳንዶ ተገቢውን ሽፋን አይሰጡም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በመንግስት በኩል የሚደረገው እገዛ አነስተኛ መሆኑን ነው የተናገሩት። ለስፖርቱ የሚደረገው የበጀት ድጎማ አንድ ውድድር ለማካሄድ እንደማይበቃ በመጠቆም የድጋፉን አናሳነት ያስረዳሉ፡፡
‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ ውድድሮች ተወዳዳሪው ራሱ ከኪሱ በማውጣት የሚሳተፍበት አጋጣሚ በርካታ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ስፖርቱ በሶስት የተለያዩ ማህበራት መከፈሉ ሌላው ችግር ነው›› ብለው ይህም ለስፖርቱ ዕድገት የሚረዱ ውድድሮች እንዲጓተቱና እንዲቋረጡ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ኢንስትራክተር አብዲሳ እንደሚሉት በኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ፌዴሬሽን አስተናጋጅነት የኢትዮጵያ ክለቦች ሻምፒዮና እና የክልል ክለቦች ሻምፒዮና ይካሄድ ነበር፡፡ ይህም ስፖርቱ ያለበትን ቁመና ለመገምገም ያግዛል፡፡ እነዚህ ውድድሮች ግን አሁን እየተካሄዱ አይደለም፡፡ የክለቦች ሻምፒዮናው ከ1996 ዓ.ም፤ እንዲሁም የኢትዮጵያ የክልሎች ሻምፒዮና ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ አልተካሄዱም።
ለውድድሮቹ መቋረጥና አለመካሄድ በባለሙያዎቹ መካከል የተፈጠረው የእርስ በርስ አለመግባባት በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡ ይህም ክፍተት በስፖርቱ ላይ የራሱን ጥቁር አሻራ አሳርፏል፡፡ ስፖርቱም እንደ አገር ራሱን የቻለ ተቋም (አካል) እንዳይኖረው አድርጓል፡፡
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ታዲያ የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ አሶሴሽን በራሱ ወጪ የተቋረጡትን ውድድሮች አካሂዷል፡፡ በዚህም ከ14 ዓመት በኋላ የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮናን፤ ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ የኢትዮጵያ ክልሎች ሻምፒዮና እንዲካሄዱ አድርጓል፡፡ አሶሴሽኑ ከእነዚህ ውድድሮች ጎን ለጎን ከየክልሉ ለተውጣጡ ለ450 አሰልጣኞች የሙያ ማሻሻያ ስልጠና በመስጠት ለስፖርቱ እድገት የበኩሉን ማበርከቱን ኢንስትራክተር አብዲሳ ይናገራሉ፡፡
ማህበሩ ሚያዚያ 21 እና 22 ቀን 2010 ዓ.ም ውድድር አካሂዷል፡፡ በውድድሩ 31 የቴኳንዶ ክለቦች የተሳተፉ ሲሆን ከእነዚህም 26 ነባር ሲሆኑ አምስቱ አዳዲስ ክለቦች ናቸው፡፡ ከሰባት ክልሎች የተውጣጡ 154 ሴቶች እና 240 ወንዶች በድምሩ 394 ስፖርተኞች ተሳትፈዋል፡፡ ተወዳዳሪዎቹ ከአረንጓዴ ቀበቶ እስከ አራተኛ ዳን ያሉ ናቸው፡፡ እነዚህም በስፓሪንግ፣ በፓተርን እና በትራዲሽናል ስፓሪንግ የተሳተፉ ናቸው፡፡ በውድድሩ አጠቃላይ ውጤት ሪል ዋርየር ቴኳንዶ ክለብ አንደኛ፣ ጆስ ቴኳንዶ ክለብ ሁለተኛ፣ እንዲሁም ቾይ ሆንግ ሂ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል፡፡
በፌዴሬሽን ደረጃ ቀደም ሲል ሲዘጋጁ የነበሩ ውድድሮች ቢቋረጡም ማህበሩ የሚያካሂዳቸው ውድድሮች ለስፖርቱ ማደግ የበኩሉን አስተዋፅዖ ያበረክታል፡፡
ቴኳንዶ በውድድር ሚዛን
የቴኳንዶ ደረጃ እና ዕድገት መለኪያው ውድድር ነው። የኢትዮጵያ ቴኳንዶ ስፖርት ደረጃ ሲመዘንም ልኬቱ ከውድድር ተሳትፎ አያልፍም፡፡ ይህን የውድድር ተሳትፎ ኢንስትራክተር ኤልያስ በሁለት መልኩ ያስቀምጡታል። የመጀመሪያው አህጉራዊ ውድድርን መሰረት ያደረገው የአፍሪካ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ሻምፒዮና ነው፡፡ እስካሁን ስድስት ጊዜ የአፍሪካ ቴኳንዶ ሻምፒዮና ተካሂዷል። አምስቱ ኢትዮጵያ ላይ ነው የተካሄዱ ሲሆን፤ስድስተኛው ብቻ ከኢትዮጵያ ውጭ በደቡብ አፍሪካ ተካሂዷል።
‹‹ኢትዮጵያ ላይ የተካሄዱትን ሁሉንም ውድድሮች በሻምፒዮናነት ነው ያጠናቀቅነው። በደቡብ አፍሪካው ውድድር ላይ ለመሳተፍ የይለፍ ፈቃድ (ቪዛ) ለማግኘት ባለመቻላችን አልሄድንም›› ያሉት ኢንስትራክተር ኤልያስ በወቅቱ በደቡብ አፍሪካ ተከስቶ የነበረው የመጤ ጠል (ዚኖፎቢያ) ግጭት የይለፍ ፈቃዱን ለማግኘት አስቸጋሪ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡ በተሳተፉባቸው ውድድሮች ቀዳሚ በመሆን ማጠናቀቃቸው ጥሩ ብቃት ላይ የመገኘታቸው ማሳያ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ኢንስትራክተር አብዲሳ ረጋሳ ፤የቴኳንዶ ስፖርት ዕድገት በክህሎት ደረጃ ሲመዘን ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ ደርሷል ይላሉ። በአገርና በአህጉር ደረጃ ብዙ ጥቁር ቀበቶ በማስመዝገብ ኢትዮጵያ የተሻለ ደረጃ ነች፡፡ ከዓለም እስከ አምስተኛ ደረጃ ውስጥ ለመግባት ችላለች፡፡ ይህም ሆኖ ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ብዙ ቀሪ የቤት ስራዎች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ። ከዚህ በተጨማሪ በኢንስትራክተሮች ቁጥር ከአፍሪካ በቀዳሚነት ለመሰለፍ ተችሏል ብለዋል፡፡ እሳቸው ባሉበት ማህበር ብቻ ከ50 በላይ ኢንተርናሽናል ኢንስትራክተሮች መኖራቸውን በማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡ የዲግሪ ደረጃ የደረሱ ባለሙያዎች መኖራቸውንም ያክላሉ፡፡
ኢንስትራክትር ኤልያስ ደግሞ፤ አገሪቱ በዓለም ሻምፒዮና ላይ ያላትን ተሳትፎና ያገኘችውን ውጤት እንዲህ ያስቀምጣሉ፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ሻምፒዮና መሳተፍ የጀመረችው እኤአ በ2013 በስፔን በተካሄደው ውድድር ነው። በውድድሩ 13 የልዑካን ቡድን ወደ ስፍራው የተጓዘ ሲሆን ተስፋ ሰጪ ውጤት ተመዝግቧል፡፡ በአጠቃላይ ውጤት ሜዳሊያ ውስጥ መግባት ባይቻልም በተለይም በስፕሪንግ እና በፓተርን ውድድር ሁለት ዙሮችን መጓዝ መቻሉ በጥንካሬ ይጠቀሳል፡፡ የተሻለ ልምድ ለመቅሰምም መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡
እአአ በ2015 በጣሊያን ኦስሎ በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና ለሁለተኛ ጊዜ መሳተፍ ተችሏል፡፡ በዚህ ውድድር ጥሩ ተፎካካሪ ከመሆን ያለፈ የመጣ ውጤት የለም፡፡ አምና በአየርላንድ ደብሊን ከተማ በተካሄደው ውድድር መሳተፍ ቢቻልም እአአ በ2013 ከተገኘው ውጤት የተሻለ ነገር ማስመዝገብ አልተቻለም፡፡
በቀጣይ እአአ በ2019 በአውስትራሊያ በሚካሄደው የዓለም ሻምፒዮና ውድድር ላይ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ባለፉት የውድድር ዓመታት ላይ የተገኙትን ልምዶች በመቀመር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ይሰራል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥሩ ተፎካካሪ በመሆን ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል፡፡ ለዚህ የሚረዱ የቤት ሥራዎችን ማከናወን ይገባል፡፡

 

 የወልዲያ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ዳግም ቅሬታ አቀረበ 

 

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያስተላለፈው የቅጣት ማሻሻያ ውሳኔ ዳግም ሊታይልኝ ይገባል ሲል የወልዲያ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ገለጸ።
የወልድያ እግር ኳስ ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገረመው ካሣ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በፕሪሚየር ሊጉ 2ኛ ዙር ጨዋታ ላይ ወልዲያ ከተማ ከፋሲል ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ ክለቡ ጥፋት መፈጸሙን ተከትሎ ያስተላለፈውን የተጋነነ ቅጣት ማሻሻያ ማድረጉ ተገቢ ነው። ፌዴሬሽኑ በቅጣት ማሻሻያው ላይ አሁንም በድጋሜ ሊመለከታቸው የሚገቡ ነጥቦች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ከሜዳ ምርጫ ጋር ተያይዞ በተላለፈው ውሳኔ ላይ ቅሬታ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

የወልዲያ ከተማ እግር ኳስ ክለብ


‹‹ ክለቡ ሦስት ጨዋታዎችን ከ500 ኪሎ ሚትር ርቆ እንዲጫወት የተላፈውን ውሳኔ ብንቀበለውም ፌዴሬሽኑ በፈለገው ሜዳ እንድንጫወት ማድረጉ ተገቢ አይደለም›› ብለዋል፡፡
ክለቡ በተወሰነለት ርቀት ሆኖ በመረጠው ሜዳ እንዲጫወት ማሻሻያ ሊያደርግ እንደሚገባ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
የክለቡ ተጫዋች የሆነው የብሩክ ቃልቦሬ የአንድ ዓመት ቅጣት ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ ቅሬታ ማስገባታቸውን አቶ ገረመው ተናግረዋል፡፡ በጨዋታ ወቅት ተጫዋቹ በሜዳ ላይ ምንም ዓይነት ጸብ የማነሳሳት ተግባር እንዳልፈፀመ አስታውሰው ስሜቱን በለቅሶ ከመግለጽ ውጪ ከዳኛም ሆነ ከተጫዋቾች ጋር አልተጋጨም ብለዋል። በመሆኑም ፌዴሬሽኑ በተጫዋቹ ላይ ያስተላለፈውን ቅጣት ማጽናቱ ተገቢ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡
ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት፤ ፌዴሬሽኑ ቀደም ሲል ያስተላለፈው 250 ሺ ብር የነበረው የገንዘብ ቅጣት ወደ 150 ሺ ብር ዝቅ ቢልም ሌላ 80 ሺ ብር ቅጣት እንዲከፍሉ በደብዳቤ ተገልፆላቸዋል፡፡ ይህም በወልድያ ስታዲየም በነበረው የሃዋሳ ከነማ እና ወልዲያ ከተማ ጨዋታ ወቅት፤ ደጋፊዎች ወደሜዳ መግባታቸውን ተከትሎ የተላለፈ ውሳኔ ነው፡፡ ከሃዋሳ ጋር በነበረው ጨዋታ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ በመግባት ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህን መሰሉ ተግባር በሌሎች ክለቦች ደጋፊዎች የሚደረግ በመሆኑ ወልዲያ ላይ ብቻ እንደጥፋት መቆጠር የለበትም፡፡ ይህም ሆኖ ከ18 ቀን በኋላ የቅጣት ውሳኔ ማሳለፍ ተገቢ አይደለም።


 ዳንኤል ዘነበ

Published in ስፖርት
Wednesday, 02 May 2018 19:02

ማን ነው ያልቆጠረ?

ከቢሮዋ ጠረጴዛ ላይ የተቀመጠውን የቀን መቁጠሪያ ደጋግማ እያስተዋለች ነው። የተወሰኑ ገጾችን በፍጥነት ገልጣ እንደጨረሰች የጣቶችዋ ምሪት ካሰበችው ቦታ አድርሷታል። በዚህ ወር አንድ በዓል እንዳለ ታስታውሳለች። ቁምነገሩ ይህ ብቻ አልነበረም። ዋናው ጉዳይ ይህ በዓል በየትኛው ዕለት ይውላል? የሚለው ነው፡፡
ቀጣዩን ምላሽ ለማግኘት እያንዳንዱን ቀን ተራ በተራ መፈተሽ ነበረባት። ስላሰበችው ቀን በቀን መቁጠሪያው መሀል የሚጠቁማትን ምልክት መፈለግ ጀመረች፡፡ ከቁጥሮቹ ዝርዝር ወደታች ካለው ክፍት ቦታ ላይ በቀይ ቀለም ተለይተው የተጻፉ መስመሮች መኖራቸውን አረጋገጠች።
እነዚህ ደማቅ ጽሑፎች ለእሷ የተለየ ትርጉም አላቸው። ከእይታዋ የምታገኘው እውነታ ወይ ያስደስታታል፣ አልያም ያስከፋታል። ደግነቱ የቀን መቁጠሪያው ምላሽ እሷ እንዳሰበችው ሆኗል። የጣቶችዋ ጥቆማ የተባለው ቀን በሥራ ዕለት እንደሚውል አረጋገጡላት፡፡ ይህ የሥራ ቀን ዝግ በመሆኑ በዕረፍት የምታሳልፍበትን ዕድል አጎናፅፏታል፡፡
አዎ! የ2010 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የሰራተኞች ቀን «ሜይዴይ» በዕለተ ማክሰኞ ውሏል፡፡ ይህ በመሆኑ ልቧ በደስታ እየዘለለ ነው። በዚህ ቀን ስራ ስለማይኖር ቤቷ ትውላለች፤ የምትሻውን ትከውንበታለች፡፡ ይህን እያሰበች ደስታዋን አጣጣመች። የዚህ ቀን እረፍት እንደተለየ ስጦታ ተሰማት። ልጅት ስለቀኑ ምንነትና ታሪካዊ መነሻ ለማወቅ ጊዜውም ሆነ ፍላጎቱ የላትም።
«ሜይዴይ» ማለት ሰው ይሁን አገር አልያም ሌላ ነገር እስከዛሬ ጠይቃና ተረድታ አታውቅም። እሷ የምታውቀው ይህ ቀን ከስራዋ አስቀርቶ በዕረፍት እንደሚያውላት ብቻ ነው። የምትፈልገውም ይህንኑ ነው፡፡ ይህ እውነታ ወደ ራሴ የልጅነት ዘመን ቢመልሰኝ የትምህርት ቤት ቆይታዬን ደጋግሜ አሰብኩት። የእሷን ስሜትና ሀሳብ ወደማንነቴ እርሾ መልሼም በወቅቱ ይሆን የነበረውን ሁሉ እንደ ድር ተረተርኩት።
ያኔ እንደ አሁኑ የመንግስት ሰራተኞች ሆነን በየወሩ ደመወዝ ሳናገኝ የተማሪነት ዘመናችን የተለየ ነበር። መቼም የትምህርት ቤት ትዝታን ያለፈበት ሁሉ ያውቀዋል። የጓደኝነት ፍቅር፣ የመምህራን ክብር፣ የትምህርት ጉጉትና ሌላውም በቀላሉ የሚረሳ አይደለም። በእኛ ዘመን ደግሞ መምህራኖቻችን እንደ እናትና አባት ይከበራሉ። እነሱም ቢሆኑ ተማሪዎቻቸውን እንደልጆቻቸው ነው የሚወዱት፤ የሚገስፁት።
ከሁሉም ግን ዛሬም ድረስ ግርም የሚለኝ የትምህርት መጀመሪያ የሆነው ዕለተ ሰኞ ሲመጣና የሳምንቱ ማጠናቀቂያ አርብ ሲደርስ የሚኖረው ተቃራኒ ስሜት ነው። ሁሌም ሰኞ ሰኞ ቀን ተማሪው በነቃ ስሜት ይታያል። በዚህ ዕለት ንጽህናውን ጠብቆ፣ ራሱን ለትምህርት አዘጋጅቶና የተሰጠውን የቤት ስራ አጠናቆ የሚመጣውም በርከት ይላል።
ማክሰኞና ዕሮብን ተሻግሮ ሀሙስ መዳረሻ ሲሆን ዕለተ አርብን የሚናፍቀው ጥቂት አይደለም። አርብ የሳምንቱ ማጠናቀቂያ ነው። ይህን ቀን ተከትለው የሚመጡት ቅዳሜና ዕሁድ በመሆናቸውም የአብዛኞቻችን ውስጠት በደስታ ይሞላል። ለምን? ተብለን ብንጠየቅ ደግሞ መልሳችን ያው አንድ ነው። ከዚህ ቀን ጀርባ ያሉት ሁለት ቀናት እረፍትን ይዘው ስለሚመጡ በእጅጉ እንወዳቸዋለን።
ቀን መቁጠሪያ የሚዘጋቸው በአላት ቅዳሜና ዕሁድ መዋላቸውን ስናውቅ በእጅጉ እንናደዳለን። በእነዚህ ቀናት ተአምር እንሰራ ይመስል በስራ ቀናት ያለመዋላቸው ጉዳይ ከልብ ያስቆጨናል። የሚገርመው ደግሞ ልክ እንደሳምንቱ የመጨረሻ ቀን ሁሉ የትምህርቱን የመጨረሻ ክፍለ ጊዜንም በጉጉት መጠበቃችን ነው። ከክፍለ ጊዜውም የመጨረሻዎቹ ጥቂት ደቂቃዎች የተለየ ደስታን ያጭሩብናል። ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን የዕለቱ ውሏችን ስላልተመቸን አልያም ትምህርቱን ስለማንወደው አልነበረም። አሁንም የሁላችንም ምክንያት የሚሆነው ከዚህ በኋላ የሚኖረው ጊዜ ወደቤት የሚኬድበትና እረፍት የምናገኝበት በመሆኑ ነው።
ሁሌም የትምህርት ጊዜንና ተያይዞ የሚኖሩትን የእረፍት ቀናት ስናስብ ለሁሉም ተማሪ የዓመቱ መጨረሻ የሆነውን የሰኔ ወርን አንዘነጋውም። ይህ ወር ተማሪዎች እንደጎበዝ አርሶ አደር የልፋታቸውን ፍሬ የሚያፍሱበት ወሳኝ ጊዜ ይሆናል። ወቅቱ ዓመቱን ሙሉ ዕውቀትን ሲቀስሙ የቆዩ ጎበዞች የሚልቃቸውንና የሚልቁትን ለይተው የሚያውቁበትም ጊዜ ነው።
ከዚህ ፉክክርና የውጤት ልዩነት በስተጀርባ ግን አሁንም በአብዛኞቻችን ህሊና ጉጉት የሚያጭር አንድ እውነት ይኖራል። ውጤታችን ምንም ይሁን ምን ተከታዮቹ ሁለት ወራት ለእኛ የተለዩ ስጦታዎቻችን ናቸው። እነዚህ ጊዜያት ረዘም ያሉ የእረፍት ቀናትን ስለያዙ በእጅጉ እንወዳቸዋለን፤ እንናፍቃቸዋለን። ወዳጆቼ! እንግዲህ ይህ ሳይሰሩ የማረፍ ጉጉት የተጠናወተን ገና ህይወት ሳያደክመን፣ በኑሮ ውጣውረድ ሳንባዝንና «ምንተይዞ ጉዞ »በምንባልበት አፍላው ዕድሜያችን ላይ ነበር።
እውነት ለመናገር በዚህ ዕድሜ እረፍትን የምንሻበት፣ ለእንቅልፍም ወደ አልጋ የምንሮጥበት ጊዜ አልነበረም። አብዛኞቻችን ከወላጆቻችን እቅፍ ያልወጣን እንደመሆኑ ስለነገው ማንነታችን ዕንቅልፍ አጥተን የምንተጋበት ሊሆን ይገባ ነበር። በእርግጥ ከብዙዎቻችን መሀል በጣት የሚቆጠሩት « ነገ ትምህርት የለም» ሲባል ይከፋቸው እንደነበር አስታውሳለሁ። እነዚህኞቹ አንዲት ደቂቃም ብትሆን ያለቁምነገር እንድትባክን አይፈልጉም። አስተማሪ ሲቀርም ሆነ ከሰአቱ ሲዘገይ ‹‹ለምን?›› ሲሉ መሟገታቸውም አይቀሬ ይሆናል።
ይህ የትምህርት ቤት ትዝታ እንደየሰው ማንነትና የጊዜ ሁኔታ ሊለያይ ይችላል። አብዛኞቻችንም ካሳለፍነው ጓደኝነትና በርካታ አጋጣሚዎች አንጻር ሁሌም በትውስታ የምንመሰጥበት የተለየ አጋጣሚ ይኖረናል። ያም ሆነ ይህ ግን አብዛኛው ተማሪ በሚያሳልፈው የትምህርት ቆይታ የአንዲቷ ቀን ትምህርት ቤት መዘጋት የሚሰጠውን ደስታና ፈንጠዝያ መቼም የሚረሳው አይመስለኝም ።
ትርጉም የለሽ ደስታው ዘመናትን ተሻግሮ አሁን ባለንበት ዘመንም ተመልሶ መምጣቱ የሚያስገርም ነው። አሁን ላይ አብዛኞቻችን በተሰማራንበት ሙያ ስራ ይዘን ደመወዝ እየተከፈለን ሊሆን ይችላል። በዕድሜና በዕውቀት በልጽገንም ከእኛ የሚጠበቅብንን ሀገራዊ ግዴታ እየተወጣን ይሆናል። እንዲህ ሲሆን ደግሞ ማንኛችንም መብትና ግዴታችንን ጠንቅቀን እናውቃለን። ከትናንቱ ያልበሰለው ልጅነታችን በተሻለም የላቀ ውጤት እንደሚጠብቀን አናጣውም።
ወዳጆቼ! አሁንም ግን ያቺ በልጅነታችን አብራን ያደገችው እረፍትን የመሻት ልማድ ከእኛ አልተነጠለችም። ዘንድሮም «ነገ እኮ ስራ የለም» ሲባል «እሰይ! ጎሽ!››እያልን እንፈነጥዛለን። ዛሬም የቀን መቁጠሪያችንን ይዘን በብሄራዊና ሀይማኖታዊ በዓላት መከበር ምክንያት የሚዘጉ ቀናትን እንለያለን። ይህን ስናደርግ የምናስባቸው በአላት ቅዳሜና ዕሁድ የሚውሉ ከሆነ ውስጣችን ይከፋል።
ሁላችንም እንደምናውቀው በትላንትናው ዕለት ዓለም አቀፉ የሰራተኞች ቀን ተከብሮ አልፏል። ይህ መሆኑ ደግሞ ከበዓሉ መታሰቢያነት ይልቅ ቀኑ ማክሰኞ ላይ መዋሉ ብዙዎቻችንን አስደስቷል። ይህን ታሪካዊ ዕለት በስራ የሚያከብሩና የቀኑን ትርጓሜ በተግባር የሚያሳዩ ሠራተኞችና አገራት እንደማይጠፉ እገምታለሁ።
እንደው ግን በሞቴ ማንኛችን እንሆን ? እነዚህን ቀናት እያሰብን እረፍትን ያልተመኘን? ማንስ ይሆን ካላንደሩን ይዞ እነዚህን ወርቃማ የሚላቸውን ቀናት እያሰበ ያልቆጠረ ?ያላስቆጠረ? በእርግጠኝነት ‹‹እኔ አለሁ›› የሚል ከተገኘ የሁልጊዜም አድናቂውና አክባሪው ልሆን ዝግጁ ነኝ ።
አጋጣሚ ሆኖ ከሌሎች ይልቅ በያዘነው ሚያዝያ ወር የሚከበሩ ሃይማኖታዊና ብሔራዊ በዓላት ይበዛሉ። ይህን የምናውቅ ብዘዎቻችንም በቀይ የተለዩ ቀናትን ከመቁጠሪያችን እየፈለግን የቀኖቹን ዕለት መመረመር ልማዳችን መሆኑ አያከራክርም። የአሁኑ የአርበኞች ቀን መታሰቢያ ቅዳሜ ሚያዝያ 27 ቀን መዋሉ በሥራ ቀን እንዲውል ለሚናፍቁ ቅሬታን መፍጠሩ አይቀርም፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

Published in መዝናኛ

በ1943 ዓ.ም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት  የደረሳትን ጥሪ  የተቀበለችው ኢትዮጵያ በኮርያ ልሳነ ምድር የተቃጣውን ጦርነት ለመከላከል የቃኘው ሻለቃ ጦሯን አሰማራች። በወቅቱ ብቸኛዋ ጥቁር አፍሪካዊት ሀገር በመሆኗ ግዴታዋን በብቃት እንደማትወጣ የገመቱ በርካቶች ነበሩ። ሆኖም ግን ያለምንም ምርኮ ጦርነቱን በድል በማጠናቀቅ ዓለምን አስደመመች። የአዲስ ዘመኗ መልካምሥራ አፈወርቅም ከዛሬ 67 ዓመት በፊት ወደ ኮርያ ከዘመቱ አርበኞች ጋር በነበራት ቆይታ በወቅቱ የነበረውን የዓውደ ውጊያ ውሎ በትዝታ ቃኝተው እንዲህ አውግተዋታል።

ግርማ ሞገስ የተላበሰው ሰፊ ግቢ የዕለቱን እንግዶች ተቀብሎ ማስተናገድ ጀምሯል። በስፍራው ከወዲያ ወዲህ ከሚሉት መሀል አብዛኞቹ በሀገር ባህል ልብስ አጊጠው ተውበዋል። ዘለግ ብሎ ከሚታየው ታሪካዊ ሀውልት ስር ከተሰባሰቡት ገሚሶቹ የውጭ ሀገራት ዜጎችና ዲፕሎማቶች ናቸው። በተለየ ተመስጦ ሆነው በሃሳብ የመረቁም ይታያሉ፡፡

ከእነሱ ባሻገር በተለየ የክብር ቦታ የተቀመጡትን አንጋፋዎች ዞር ብዬ አስተዋልኳቸው። አብዛኛዎቹ በዕድሜ ገፍተዋል። ባስ ያለ ድካም የሚታይባቸውም በሌሎች ድጋፍ እየተመሩ ከስፍራው ደርሰዋል። ሁሉም ይህቺን ቀን በቤታቸው ማሳለፍ የፈለጉ አይመስልም። ተናፋፍቀው የተገናኙት የዕድሜ እኩዮች ከስልሳ ሰባት ዓመታት በፊት ስላሳለፉት የጦር ሜዳ ውሎ እያስታወሱ በትዝታ ማውጋታቸውን ቀጥለዋል።
እነሱ ያንን ጊዜ በቀላሉ መርሳት አይቻላቸውም። የቃኘው ሻለቃና የኮርያው ጦርነት በማንነታቸው ታላቅ ክብር እንደያዘ ዓመታትን ተሻግሯል። የዛኔዎቹ ጀግኖች፣ የዛሬዎቹ አርበኞች አሁን ላይ ሆነው የጥንቱን ሲያወጉ ጨዋታቸው ሁሉ የጋራ ነው። አንዱ በሚያስታውሰው ላይ ሌሎቹ ሲያክሉ በተለየ ስሜትና መደማመጥ ነበር።
በ1943 ዓ.ም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አንድ አስችኳይ ጥሪ አስተላለፈ። «ደቡብ ኮርያ በጃፓን ቅኝ ግዛት ተይዛለች፣ ሰሜን ኮርያም ይህን አጋጣሚ ለመጠቀም ጦር አዝምታባታለች፣ ሀገሪቱ ከዚህ አጣብቂኝ ፈጥና መላቀቅ አለባት። ለዚህ ዕውን መሆን ደግሞ ዓለም ሊተባበራት ይገባል» የሚል፡፡
ጥሪውን ከሰሙት ሀገራት መሀል የኢትዮጵያ ምላሽ ፈጣን ሆነ። በወቅቱ የነበሩት የቃኘው ሻለቃ ጦር ወታደሮች ወደ ኮርያ ሊዘምቱ ትጥቃቸውን አዘጋጁ። በተለየ ጀግንነትና ወኔም የሀገራቸውን ባንዲራ ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እጅ ተረክበውና ባህር አቋርጠው ወደ ኮርያ ምድር ተሻገሩ።
ሻለቃ አበራ በወቅቱ የሦስተኛ ቃኘው ሻለቃ ጦር አባል ነበሩ። ወደ ኮርያ የዘመተው ጦር ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ አባላትን ይዞ እንደነበር ያስታውሳሉ። በወጣት ወታደሮች አቋም የታገዘው ሠራዊት በባቡር ተሳፍሮ ጅቡቲ ሲደርስ ይጠብቀው ከነበረው የአሜሪካ መርከብ ተሳፈረ። ሌት ተቀንም በባህር ላይ ያለማቋረጥ ተጓዘ።
ሻለቃ አበራን ጨምሮ በርካቶቹ ወታደሮች ከሃያ ሁለት ቀናት በኋላ ፑሳን ከተባለ ከተማ ሲደርሱ ተጨማሪ ወታደራዊ ልምምድ ይጠብቃቸው ነበር። ከዚህ በኋላ የሚቀረው የግንባር ውሎ ይሆናል። ይህን ለማሳካትም በጋለ ወኔና በተሻለ ወታደራዊ አቋም የጠነከረው ሠራዊት የጀግንነት ጀብዱ ለመፈጸም የነበረው ስሜት የተለየ እንደነበር ያታውሳሉ። በወቅቱ ጦሩን የሚመሩት ጄኔራል ወልደዮሐንስ ሽታዬ ነበሩ። ሻለቃ አበራም የሰማንያ አንድ ሞርታር ጓድ ኃላፊ በመሆን ተሰልፈዋል።
በወቅቱ ከጠላት ጦር ጋር በተካሄደው ውጊያ አመርቂ የሚባል ውጤት በመገኘቱ ድል ሊመዘገብ ችሏል። የዛኔ የሃያ ዓመት ወጣት የነበሩት ሻለቃ አበራ የዕለቱን የጦር ሜዳ ውሎ በዛሬው አቋማቸው ሲያስታወሱት ውስጣቸው በእጅጉ ይደሰታል። ዓመታትን ተሻግረውም በነበረው ተጋድሎና በተገኘው ወርቃማ ድል ይኮራሉ።
ሻለቃ የዛኔ አብረዋቸው የዘመቱትን ጀግኖች የተለየ ወኔ በፍጹም አይረሱትም። በወቅቱ የነበሩት የጦር መሳሪያዎች ከአሁኖቹ ጋር የሚወዳደሩ ባይሆንም የኢትዮጵያ ወታደሮች የነበራቸው አቋምና የጦር ስልት ግን ከሌሎች የሚልቅ ነበር። በአየርና በእግረኛ ጦር የነበረው ዕውቀት የተሻለ በመሆኑም ሊመዘገብ የቻለው ድል ወርቃማ ሆኖ ዛሬም ድረስ በታሪኩ ሊደምቅ ችሏል።
መቼውንም ቢሆን ማንም ዘማች ኢትዮጵያዊ እጁን ለጠላት አሳልፎ የመስጠት ልማድ እንደሌለውም ማሳያ ሆኖ ይነሳል፡፡ ጥይት አልቆ የእጅ በእጅ ግብ ግብ ቢፈጠር እንኳን የሚታገለውን ጥሎና የእጁን ምርኮ ይዞ እየፎከረ መግባት የማንነቱ መለያ ስለመሆኑ ሁሉም የሚመሰክሩት ነው። መማረክ ማለት ለአንድ ኢትዮጵያዊ ወታደር ሽንፈት ብቻ ሳይሆን ነውርም ጭምር ነበር። በመሆኑም አብዛኛዎቹ አጋር ተዋጊዎች ለጀግኖቹ የቃኘው ጦር አባላት የነበራቸው ክብር የተለየ ሆኖ ዘልቋል።
የሃምሳ አለቃ ሸዋንዳኝ ወልደየስም ከዛሬ ስልሳ ሰባት ዓመት በፊት በኮርያ ከዘመቱ ጀግኖች መሀል አንዱ ናቸው። በወቅቱ በሀገሪቱ የሠለጠነ የጦር ኃይል በመኖሩ የዘመቻውን ጥሪ ተቀብሎ ለመጓዝ የኢትዮጵያ ወታደሮች ብቁ እንደነበሩ ያስታውሳሉ። እሳቸው በመጀመሪያው ጥሪ በ1943 ዓ.ም ወደ ኮርያ ሲዘምቱ ገና የአስራ ዘጠኝ ዓመት ወጣት ነበሩ። ለሁለት ጊዜ በዘመቱበት አውደውጊያ የከባድ መሳሪያ ተኳሽና የሞርታር ዓላሚ በመሆን ግዳጃቸውን ተወጥተዋል፡፡
እሳቸው ኮርያ ሲገቡ በጦርነቱ ከተሳተፉት ሀገራት የቱርክ ወታደሮች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው በምርኮ ጭምር ተግዘው ነበር። በወቅቱ በስፍራው የደረሰው የቃኘው ጦርም ቦታውን ተክቶ ጦርነቱን እንዲረከብ ትዕዛዝ ደረሰው። ይህኔ በአዲስ ወኔ ተጠናክሮ የመጣው የኢትዮጵያ ሠራዊት የተያዘውን ቦታ ከጠላት ለማስለቀቅ የራሱን ስልት ነደፈ። በአጭር ጊዜም ስፍራውን በድል ተቆጣጥሮ አሸናፊነትን ተቀዳጀ።
የሃምሳ አለቃ ሸዋንዳኝ ከሁሉም የማይረሱት ሰባት መቶ የሚባለውን የተራራ ላይ ውጊያ ነው። በዚህ ተራራ ላይ በተደረገው ተደጋጋሚ ጦርነት ሌሎች ሀገራት በሽንፈት ወድቀዋል። ብዙዎችም እጃቸውን ለምርኮ ሰጥተው ለህልፈት ተዳርገዋል። የሀገሩ ግግር በረዶና ተቀብረው የቆዩ ፈንጂዎች ደግሞ ጦርነቱን እጅግ ፈታኝ አድርገውት እንደነበር ያስታውሳሉ።
በርካቶችም ለሞትና ለጉዳት ተዳርገዋል። የቃኘው ሻለቃ ጦር ግን በዚህ ቦታ ያሳየው ተጋድሎ በድል የታጀበ ነበር። አስቀድሞ በፈንጂ ምርመራ ላይ የነበረው ዕውቀት ራሱን ለመጠበቅ አግዞታል። በወቅቱ የኢትዮጵያውያን ጀግንነትና ያለመማረክ ጀብዱም የገነነ ነበር። ይህን የሚያውቁ ጠላቶች ደግሞ ታሪክን ለመለወጥ የማያደርጉት የለም።
በአንዱ ቀን ሰሜን ኮርያ በጦር ሜዳ ውሎ የሚተገበር ፈጣን አዋጅ አስነገረች። የኢትዮጵያን ወታደሮች ማርኮ ለሚያመጣ የጄኔራል ማዕረግ እንደምትሰጥም አሳወቀች። ይህ በሆነ ማግስት አንድ የወገን ወታደር በዓውደ ውጊያ ላይ በቦንብ ተመትቶ ቆሰለ። በቅርበት ሲያስተውለው የነበረ የሰሜን ኮርያ ወታደርም መጎዳቱን እንዳየ ከወደቀበት ጉድጓድ ፈጥኖ ደረሰ። ወዲያውም የመለያ መታወቂያውን ከአንገቱ ለመውሰድ ከባድ ትግል ገጠመው።
ዓላማውን ፈጥኖ የተረዳው ኢትዮጵያዊ ግን በቀላሉ ተሸንፎ የሀገሩን ስም ማስነጠቅ አልወደደም። እንደምንም ከወደቀበት ተነስቶ የተቀናቃኙን አንገት አንቆ ያዘ። በሁለቱ መሀል የተጀመረው ትንቅንቅም ያለገላጋይ ቀጠለ። ትግሉ ክፉኛ ቆስሎ ደሙን በሚያዘራና ምንም ባልተጎዳ ወታደር መካከል ሆነ። ያም ሆኖ ግን ኢትዮጵያዊው ወታደር የዋዛ አልሆነም። የሞት ሽረት ትግሉን ቀጠለ። በያዘው ሳንጃም የጠላቱን አንገት ቀልቶ ከጎኑ ወደቀ። በዚህ መስዋዕትነት በቀለመው ደሙም የሀገሩን ታሪክ ሳያስነጥቅ ስሙን አድምቆ ጻፈ።
አንዴ ደግሞ በዚሁ የዓውደ ውጊያ ውሎ አስገራሚ የሚባል ታሪክ ተፈጸመ። የሃምሳ አለቃ ደቦጭ በርበሬ የሚባል ወታደር በማቀዝቀዣ የቆየ ጉማጅ ሥጋ በቦርሳው ይዞ ወደ ውጊያው ሜዳ ገሰገሰ። በወቅቱ ከጠላት ጋር ጦርነቱ ተፋፍሞ ነበር። ለሰዓታት የቆየው ፍልሚያ አይሎ ሲጠናከርም የጨበጣ ውጊያው ቀጠለ። መታገሉ፣ ሳንጃ ለሳንጃ መሞሻለቁና መጣል መውደቁ በረታ።
የሃምሳ አለቃ ደቦጭን የገጠመው ወታደር ጉልበቱን ፈትኖ ተገዳደረው። በእጅ በእጅ ውጊያ ልዩ ስልት የነበረው የያኔው ወጣቱ ደቦጭ ግን ጠላቱን በሰደፍ በመጣል ለምርኮ ዳረገው። ወዲያውም በቦርሳው የያዘውን ጥሬ ሥጋ አስታወሰ። በምርኮኛው ትከሻ ላይ ተቀምጦም ሥጋውን እየቆረጠ ደጋግሞ ጎረሰ። ይህን ያየው ምርኮኛውና ሌሎችም በሆነው ነገር ሁሉ በጣም ተረበሹ። ወታደሮቹ የሰው ሥጋ እንደሚበሉ ተረድተውም በድንጋጤ በረገጉ። ምርኮኛው በግዞት ከቆየበት የጦር ሰፈር ተለቆ ወደነበረበት ሲመለስ «ኢትዮጵያውያን ወታደሮች የሰው ሥጋ ይበላሉ» በሚል ወሬውን ነዛው። ይህ ተጽዕኖም በሌሎች ተዋጊዎች ጭምር ሽብርና ስጋት ሆኖ ሰነበተ።
የወሬውን መስፋፈት የሰሙ የጦር አዛዦች ግን ይህ ስም ሊለወጥ እንደሚገባ ተስማሙ። የተወራው ሁሉ ሀሰት እንደሆነም በበራሪ ወረቀት በትነው አስታወቁ። የአሜሪካ መንግሥትም የተባለውን ለማስተባበል እገዛ አደረገ። በወቅቱ አምስት መቶ የወገን ጦር ቁስለኞች መኖራቸውን የሃምሳ አለቃ ሸዋንዳኝ ያስታውሳሉ። በጦርነቱ አንድ መቶ ሃያ ሁለት ወታደሮችም መስዋዕት ሆነዋል። በምርኮ የተወሰደ አንድም ወታደር ያለመኖሩ ግን ዛሬም ድረስ ያኮራቸዋል።
በቅርቡ 67ኛው ዓመት የኮርያ ዘማቾች መታሰቢያ ዕለት ተከብሯል። ዕለቱ ጀግኖች አርበኞች በድል የተመለሱበትና የተረከቡትን ሰንደቅ ዓላማ ለንጉሠ ነገሥቱ መልሰው ያስረከቡበት በመሆኑ የተለየ ክብር ተሰጥቶታል። በወቅቱ የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መለሰ ተሰማም የቀደመው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ዛሬ ድረስ መቀጠሉ ለሀገራችን ታላቅ ኩራትና ክብር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በኮርያ ልሳነ ምድር ያስመዘገቡት ድል ዛሬም በኮርያውያን ዘንድ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ በኢትዮጵያ የደቡብ ኮርያ አምባሳደር ሊም ሁን ሚን «የኢትዮጵያውያን ብዙ ዕዳ አለብን» ይላሉ፡፡ ለደቡብ ኮርያ ነፃነት ሲባል ውድ ህይወታቸውን ለከፈሉና በጀግንነት ለተሰለፉ አርበኞች ሁሉ ታላቅ ክብር እንዳላቸው ተናግረዋል። በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው መልካም ወዳጅነትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል።
በመታሰቢያ በዓሉ ላይ በርካታ የደቡብ ኮርያ ተወላጆችና ሌሎች የውጭ ሀገራት ዜጎች በእንግድነት መገኘታቸውን አስተዋልኩ። በተለምዶ አፍንጮ በር ከሚባለው አካባቢ እልፍ ብሎ በሚገኘው ናይጄሪያ ኤምባሲ አቅራቢያ በሚገኘው የኮርያ ዘማቾች መታሰቢያ ፓርክ ውስጥ ለዘማቾቹ መታሰቢያ እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡ በተለይም በጦርነቱ ዘምተው ህይወታቸውን የሰዉና 122 ጀግኖች ከ67 ዓመት በፊት አፅማቸው ወደ አገራቸው ተመልሶ እንዲያርፍ የተደረጉ ጀግኖች በየስማቸው ሀውልት ቆሞላቸዋል፡፡ ከሁሉም ግን የእነዚህ አርበኞች ስም በፋኖ የክራር ትዝታ ታጅቦ ሲዘረዘር የነበረው ስሜት የተለየ ነበር። ስም ከመቃብር በላይ ይውሏል እንዲሉ ከኮርያ ተራሮች ግርጌ የደመቀው ታሪክ ዛሬም እንዲህ ደምቆ መታወሱን ቀጥሏል።

 

Published in ማህበራዊ
Wednesday, 02 May 2018 18:51

ሰብዓዊ መብት በኢትዮጵያ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሰብዓዊ መብት አከባበር ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ስም ሁሌም በአሉታዊ መልኩ ይነሳል፡፡ኢትዮጵያ በአንድ በኩል ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበች የምትገኝ ተብላ በዓለም አቀፍ ተቋማት ብትሞገስም በሌላ ጎኑ ደግሞ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት አታከብርም በሚል ትተቻለች፡፡ ይህ ትችት ይጋነን እንደሆነ እንጂ እውነታ መሆኑን የተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች በተደጋጋሚ ይገልፃሉ፡፡ መንግስትም ችግሩ መኖሩን ሲገልፅ ይደመጣል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግና አስተዳደር ኮሌጅ የሰብዓዊ መብት መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ታደሰ ካሳ ሰብዓዊ መብት ሰፊ ጸንሰ ሀሳብ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ፅንሰ ሃሳቡ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ፣ ሲቪልና የፖለቲካ ሰብዓዊ መብቶችን እንደሚያካትት ይገልፃሉ፡፡
ከፖለቲካና ከሲቪል ሰብዓዊ መብቶች ጋር ተያይዞ መንግስታት ብዙ ጊዜ ስማቸው በተደጋጋሚ እንደሚነሳና እንደሚከሰስ ዶክተር ታደሰ ያመለክታሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በደካማ ጎን ስሙ ከሚጠቀስባቸው ጉዳዮች የሲቪልና የፖለቲካ ሰብዓዊ መብት ችግሮች ይጠቀሳሉ፡፡ ከእነዚህ ደግሞ ሀሳብን በነጻነት የመግለፅ፣ የመደራጀት ፣ የመንቀሳቀስ፣ በፖለቲካው የመሳተፍ፣ የደህንነት መብትና በህይወት የመኖር መብቶች ይገኙበታል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ለሰብዓዊ መብት የሰጠችው ትኩረት በህገ መንግስት ደረጃ ችግር የለበትም፡፡ ሊበራል ከሚባሉት አገራት የሚመደብ ህገ መንግስት ብቻ ሳይሆን የዜጎች መብቶችና ነጻነቶችን የሚያከብሩና እንዲከበር የሚጠይቁ ድንጋጌዎች የያዘ ነው፡፡ ሆኖም ግን በህጉ እውቅና የተሰጣቸው ሰብዓዊ መብቶች በተሟላ መልኩ ተፈጻሚ አይሆኑም››ይላሉ፡፡
በአፈጻጸም ችግር የተነሳ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መኖራቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ግለሰቦችና የተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች ብቻ ሳይሆኑ መንግስትም ያመነው ጉዳይ እንደሆነ ዶክተር ታደሰ ይገልፃሉ፡፡ የገዥው ፓርቲ የቅርብ ጊዜ ስብሰባዎች ሪፖርት ከሚዳስሳቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑን በማጣቀሻነት ያቀርባሉ፡፡
መንግስት ሰብዓዊ መብትን በተመለከተ መሰረታዊ ህጸጾችን መፈጸሙን የሚናገሩት ዶክተር ታደሰ እነዚህም ከሙስና፣ ከአስተዳደር ችግርና ብልሹ አሰራሮች ጋር እንደሚያያዙ ይጠቁማሉ፡፡ በተለይ በፖሊሲ ተቋማት፣ ፤ፍርድ ቤቶችና ማረሚያ ቤቶች በአንድ ሆነ በሌላ መልኩ የግለሰብን ነጻነት የሚጎዱ ችግሮች ይታያሉ ብለዋል፡፡
‹‹ተቋማዊ አደረጃጀትን በመፍጠርና፣ ህግን በማውጣት ረገድ ኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግር የለባትም››ያሉት ዶክተር ታደሰ፤ የመንግስት ዓመታዊ ግምገማዎች የአፈጻጸም ችግሮችን ቢያመላክቱም ችግሮቹ ከመፈታት ይልቅ ሲባባሱ ይታያል፡፡ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ድረስ በየደረጃው መሰረታዊ የሚባሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖራቸው ግልፅ ነው፡፡ ፖሊስ በህግና በህገ መንግስቱ የተወሰነ ስልጣን እንዳ ለው ቢታወቅም በህግ የማይደገፉ አያያዞችን ሲጠቀም እንደሚታይ ነው ዶክተር ታደሰ ያስረዱት፡፡ በፍርድ ቤቶች የሚስተ ዋለው ሙስናም ሌላው ችግር ነው፡፡
የተቋሞች የአቅም ውስንነት፣ የሀብት አለመኖር፣ በህገ መንግስቱ የተካተቱ የሰብዓዊ መብት ድንጋ ጌዎችን በመንግስት በኩል ማስፈጸም የሚያስችል ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት አለመኖር ክፋተቶቹን ለመፍታት ያልተቻለባቸው ምክንያቶች መሆና ቸውን ዶክተር ታደሰ አስረድተ ዋል፡፡
የመልካም አስተዳደር ችግር ገዝፎ ህብረተሰቡ ሮሮ ሲያሰማ አንድ ሰሞን የሙስና ጉዳይ በሚዲያና በህብረተሰቡ ይራገባል፡፡ መንግስት አራት፣ አምስት ባለስል ጣን ያስራል፡፡ ችግሩን ለመፍታት ትንንሽ እርምጃዎችን ይወስዳል፡፡ ችግሩን ስር ነቀል በሆነ መልኩ ለማስወገድ የሚያስችል የፖለቲካ ቁርጠኝነት አለማሳየቱን ዶክተር ታደሰ ይተቻሉ፡፡ እናም የሰብዓዊ መብትን በተሟላ መልኩ ለማስከበር መንግስት ቁርጠኛ መሆን ይኖርበ ታል፡፡
ለዶክተር ታደሰ የተቋማት የአቅምና የአመራር ችግር ለሰብዓዊ መብት አለመከበር መንስኤ አይሆንም? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ ‹‹የተቋማትና የአመራር አቅም ማነስ ትንሽ ችግር እንጂ ዋናው አይደለም፡፡ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት የሚመደቡ ኃላፊዎች መሰረታዊ አጀንዳቸው በተቋሙ ውስጥ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ነው፡፡ነገር ግን በአቅም ማነስ ሳቢያ አገልግሎት ሊያቀላጥፉ ይቅርና የሚያባብሱበት ሁኔታ ይስተዋላል›› ብለዋል፡፡
ሰብዓዊ መብት የሁሉም ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎትና ጥያቄ ስለሆነ መከበር አለበት፡፡ ሰብዓዊ መብት አንዱ የዴሞክራሲ ቅርጫፍ እንደሆነ የሚገልፁት ዶክተር ታደሰ፤ መንግስት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት አላከበረም ማለት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የለም እንደማለት ነው ይላሉ፡፡ ስለዚህ መንግስት የዴሞክራሲ ስርዓትን ማስፈን ካልቻለ ረጅም ጊዜ በስልጣን መቀጠል አይችልም፡፡ ምክንያቱም ከህዝብ ፍላጎትና ስሜት ጋር አብሮ መሄድ አልቻለምና፡፡
የዴሞክራሲ ችግር ያለበት አገር ለግጭትና ለመፈራረስ የቀረበ ነው፡፡ ስለዚህ ዴሞክራሲ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ለዚህ ማሳያው ደግሞ ባለፉት ሁለት አመታት በአገሪቱ የተከሰቱት ግጭቶች ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ለሰላም ምን ያህል ዋጋ እንዳላቸው አመላካች ናቸው ብለዋል-ዶክተር ታደሰ፡፡
የሰብዓዊ መብት አለመከበር የሚያመጣውን ጦስ ዶክተር ታደሰ እንዲህ ያብራራሉ፡፡ የዜጎች ሰብዓዊ መብት ካልተከበረ እንደ አገር ለመቀጠል ያለውን ህልም ያጨልማል፡፡ ህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጡት ወርቃማ መብቶች ተግባራዊ እንዳይሆኑ ያደርጋል፡፡ በዜጎች ላይ አእምሯዊና አካላዊ ጉዳት እንዲከሰት በር ይከፍታል፡፡ይህም በፖለቲካ ስርዓቱ ላይ ትልቅ አደጋን ይደቅናል፡፡ እየባሰ ሲሄድ አገርን ያፈርሳል፡፡
በህገ መንግስቱ የተደነገጉትን የሰብዓዊ መብት፣ የመልካም አስተዳደርና የህግ የበላይነት ድንጋጌዎችን የሚያስፈጸም ተቋም መገንባትና ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህ አለመሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲስተዋሉ ማድረጉን የጀስትስ ፎር ኦል (ፍትህ ለሁሉም) ተቋም ፕሬዚዳንት ፓስተር ዳንኤል ገብረስላሴ ይናገራሉ፡፡
በተለይ የሰብዓዊ መብት አያያዝ በማረሚያ ቤቶች እያተሻሻለ ቢመጣም በአንጻሩ በምርመራ ጊዜ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚደርስባቸው ብዙ ታራሚዎች ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡ በምርመራ ወቅት በወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት ማድረስን ስርዓቱ ባይፈቅድም የተወሰኑ ግለሰቦች የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈጽሙ ማስተዋላቸውን ፓስተር ዳንኤል ገልፀዋል፡፡
የሰብዓዊ መብት ጥሰት በኢኮኖሚው ላይ የሚያደርሰው ጫና ይኖራል? ለሚለው ጥያቄም ፓስተር ዳንኤል የሚሉት አለ፡፡ ኢኮኖሚው የሚመራው በህግና በስርዓት ነው፡፡ ህግና ስርዓት ካልተከበረ ኢኮኖሚው ሊያድግ አይችልም፤ ቢያድግም እንኳ ኢኮኖሚው ፍትሀዊ አይሆንም፡፡ በተለይ የውጭ ባለሀብቶች ኢንቨስት ከማድረጋቸው በፊት በአገሪቱ ውስጥ የህግ የበላይነት መኖሩን ያረጋግጣሉ፡፡
ስለሆነም መንግስት ሊወስዳቸው የሚገቡ እርምጃዎችን እንዲህ ያሳቀምጣሉ፡፡ በምርመራም ሆነ በማረሚያ ቤቶች የሰብዓዊ ጥሰት የሚፈጸሙ ግለሰቦችን ተከታትሎ እርምጃ መወሰድ ይገባል:: በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የህዝቡንም ንቃተ ህሊና ማሳዳግ ይጠበቃል ፡፡ ህዝቡ ፍትህ ሳይሸራረፍ ተጠቃሚ እንዲሆንና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፤ የፍትህ ተቋማት ያለምንም ተፅእኖ ተልኮቸውን እንዲወጡ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
‹‹የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ይፋ አድርገዋል፡፡ይህ ህዝቡ ተስፋ እንዲሰንቅ አድርጓል›› ያሉት ፓስተር ዳንኤል፤ እነዚህ ተስፋዎች እውን የሚሆኑት እሳቸው የሚሰጡትን አቅጣጫዎች የፍትህ ተቋማት ተቀብለው ሲተገብሩት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለምታከናውነው የሰብአዊ መብት አያያዝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ድጋፍ እንደሚያደርግ ሰሞኑን ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ኮሚሽነር ዛይድ ራድ አል ሁሴን ገልጸዋል፡፡ ሰብዓዊ መብትን ለማስከበር ትክክለኛ አቅጣጫ መያዟን ጠቁመው አሁንም በሰብአዊ መብት አያያዝ ረገድ ብዙ መስራት እንዳለባት አስገንዝበዋል፡፡
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በበኩላቸው ኮሚሽነር ዛይድ ራድ አልሁሴን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ጋር ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብትን ለማስከበር ስር ነቀል ለውጦች እያካሄደች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለፃቸውን አስታውቀዋል፡፡ በአገሪቱ የዴሞክራሲ ግንባታ፣ የመልካም አስተዳደር መስፈን እና ልማትን ማረጋገጥ አጽንኦት የሚሰጣቸው ተግባራት እንደሆኑም መናገራቸው ነው የተሰማው፡፡

ጌትነት ምህረቴ

 

 

 

Published in ፖለቲካ

ዶክተር ስንታየሁ ወልደ ሚካኤል የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪቸውን ከአስመራና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች በኢኮኖሚክስ ይዘዋል፡፡ በኦስትሪያ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኩዊንስ ደግሞ በኢኮኖሚክስ ትምህርት ዘርፍ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን (ፒኤችዲ) አግኝተዋል፡፡ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በአማራ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ቢሮ፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲና በብሄራዊ ባንክ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች በመመደብ አገራቸውን አገልግለዋል፡፡
የኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስትር በመሆን ያገለገሉ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም የመንግሥት የፋይናንስ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በኤጀንሲ አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እነሆ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኤጀንሲው የተቋቋመበትን ዓላማ ከማሳካት አንፃር እንዴት እየተጓዘ ነው?
ዶክተር ስንታየሁ፡- ከ1983 ዓ.ም በኋላ የግል ድርጅቶች በገበያ ህግ የሚመሩበት፤ ለውድድር የሚበረታቱበትና ከሌሎች ጋር ሊሰሩ የሚችሉበትን ሁኔታ ለማሳለጥ እንዲያመች ዓመታዊ የአክሲዮን ማህበር ስብሰባ ያካሄዳሉ፡፡ በዚህ ስብሰባ አማካኝነት ዕቅዳቸውን፣ በጀታቸውን፣ የዓመቱን የስራ አፈጻጸም እንቅስቃሴና የኦዲተር ምርመራን ያጸድቃሉ፡፡
ለመንግሥት የፋይናንስ ድርጅቶች ማለትም ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና ለኢትዮጵያ መድህን ድርጅት ልክ እንደ አክሲዮን ማህበር ሆኖ ማገልገል የሚችል ተቋም ያስፈልግ ነበር፡፡ ለዚህም እንዲረዳ ኤጀንሲው ተቋቁሞ እነዚህ የፋይናንስ ድርጅቶች የመንግስትን ዓላማ በትክክል መፈጸማቸውን የመቆጣጠር ኃላፊነትን ተረክቦ ወደ ሥራ ገባ፡፡
በዚህ መሰረትም ኤጀንሲው የተቋማቱን ዓመታዊ ዕቅድ፣ በጀት የኦዲት ሪፖርትና መሰል ጉዳዮችን በበላይነት ይከታተላል ፤ይወስናል፡፡ የዳይሬክተሮችን የቦርድ አባላትና የቦርድ ሰብሳቢዎችን ይሰይማል፡፡ ዓመታዊ ዕቅዳቸውንና በጀታቸውን መርምሮ ያጸድቃል፡፡ እንዲሁም ኦዲተሮችን ይሰይማል፤ የኦዲተሮችን ሪፖርት አዳምጦ ብይን ይሰጣል፡፡ የመዋህድና የመክሰም ጉዳይ ሲኖር ውሳኔ ያስተላልፋል፡፡ በተቋማቱ የመንግስትን ጥቅም ለማስከበር ይሰራል፡፡
የፋይናንስ ድርጅቶቹ አገራዊ ልማትን ለማፋጠን ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ናቸው፡፡ ድርሻቸውን የሚወጡት በምኞትና በማሰብ ብቻ ሳይሆን ጠንካራ ተቋማት ሲኖሩ ነው፡፡ ይህን ለማሳካት የተቋማቱ አሰራር ዘመናዊ መሆን አለበት፡፡ ዘመናዊ አሰራር ለማምጣት ደግሞ የሚጠቀሙበት ቴክኖሎጂ፣ የስራ ፍሰቱና የሚተገበረው ዘዴ ይወስናል፡፡ ይህ ሲሆን የተፋጠነ አገልግሎት መስጠት ይቻላል፡፡
ተቋማቱ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማፋጠን ተገቢውን ዕውቀት፣ ክህሎትና ተነሳሽነትን የተላበሰ የሰው ኃይል ያስፈልጋቸዋል፡፡ የተሟሉ ህጎችና ደንቦች ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ኤጀንሲው እነዚህ አሰራሮችና አደረጃጀቶች እንዲኖሩ ይሰራል፡፡ ተቋማቱ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት እንዲወጡ ይጥራል፡፡ በአቅም ግንባታ ስራ በመደገፍና ክትትል በማድረግ ተቋማቱ ቀልጣፋ፣ ዘመናዊና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እየሰራ ነው፡፡ በመሆኑን የተጣለበትን ኃላፊነትና ዓላማውን ለማሳካት እየተጓዘ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡-ኤጀንሲው የሚከታተላቸውና የሚደግፋቸው የፋይናንስ ድርጅቶች ያሉበት ደረጃ እንዴት ይገለፃል?
ዶክተር ስንታየሁ፡- በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ አድጓል ባይባልም የፋይናንስ ተቋማቱ የፋይናንስ ስራዎች እንዲበረታቱና እንዲያድጉ ፈር ቀዳጅ ሚና አላቸው፡፡ በገበያው ውስጥ አርአያ ሆነው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና አሰራሮችን በመዘርጋት አጠቃላይ የፋይናንስ ዘርፉ እንዲዘምን እየሰሩ ይገኛል፡፡ ተቋማቱ ትርፍ ለማግኘት ብቻ የተቋቋሙ አይደሉም፡፡ የፋይናንስ አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየተጉ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት እጅግ የተሳካ ስራ ስርቷል ብለን የምናነሳው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ነው፡፡ ባንኩ ኢትዮጵያ ውስጥ የ75 ዓመት ዕድሜ አስቆጥሯል፡፡ በተለይ ባለፉት 10 ዓመታት ተደራሽነቱን ከማስፋት አኳያ ብዙ ስራ አከናውኗል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከአንድ ሺ 200 በላይ ቅርጫፎች አሉት፡፡ ዋጋ በማረጋጋት፣ አዳዲስ አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን በመተግበር በኩልም በከፍተኛ ደረጃ እየሰራ ነው፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ለመንግሥት ትላልቅ ፕሮጀክቶች ብድር በመስጠት የመንግስት ኢኮኖሚያዊ ልማት እንዲሳካ ጥረት የሚያደርግ ትልቅ ተቋም ነው፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በወጪ ንግድ፣ በኢንዱስትሪና በግብርና ልማት ለተሰማሩ ለውጭና ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች የብድር አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በዚህም ኢኮኖሚያዊ ልማት እንዲፋጠን የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል ማለት ይቻላል፡፡
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የገበያ ድርሻው ከ40 እስከ 45 በመቶ ድረስ ቢዋዥቅም በዘርፉ ውስጥ ዋጋ በማረጋጋትና ሌሎች እንዲስፋፉ አርአያ በመሆን እየሰራ ነው፡፡ አዳዲስ ተቋማት እንዲፈጠሩ ሀሳቦችን በማመንጨት የበኩሉን አበርክቷል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ሪ ኢንሹራንስ ኩባንያ (የጠለፋ ዋስትና) እንዲቋቋም ሀሳብ በማቅረብ ሀሳቡ ተቀባይነት አግኝቶ ኩባንያው ሊቋቋም ችሏል፡፡ የፋይናንስ ተቋማቱ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ እየፈፀሙ ቢሆንም አሁን ከተደረሰበት የኢኮኖሚ ደረጃ ጋር ሲነጻጸሩ ገና ብዙ ሥራ ይቀራቸዋል፡፡
ሁለቱ ባንኮች በብድር አሰጣጥና በቁጠባ አገልግሎት ረጅም ርቀት የተጓዙ ቢሆንም በመድን ዘርፍ ግን ገና ብዙ ስራ ይቀራል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የመድን ስራ በዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ከጎረቤቶቻችንና ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲወዳደር እጅግ አነስተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ አገልግሎቱም በአብዛኛው እየተሰጠ ያለው የሀብት ደረጃቸው ከፍተኛ ለሆኑት ብቻ ነው ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የመድን አገልግሎትን አነስተኛ ገቢ ላለው የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ ምን እየተሰራ ነው?
ዶክተር ስንታየሁ፡- በገጠርና በከተማ አነስተኛ ገቢ ላለው የህብረተሰብ ክፍል አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡በተለይ ለአርሶ አደሩ ለእንሰሳቱና ለሰብሉ የመድን ዋስትና የሚገባበት ስርዓቶች እየተዘረጉ ናቸው፡፡ በከተሞችም እንዲሁ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚደርጉ የመድን ዋስትና አይነቶች የሚተገበሩ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በልማት ባንክ የብድር አሰጣጥ ዙርያ ቅሬታ ይነሳል፤ ባንኩ ያበደረውን ገንዘብ የማስመለስ አቅሙም ደካማ እንደሆነ ይገለፃል፡፡ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት?
ዶክተር ስታየሁ፡- ባለፉት ዓመታት ግብርናው ለወጭ ንግዱ ዋስትና እንዲሆንና ለኢንዱስትሪዎችም ግብዓት እንዲያቀርብ በሚል በግብርና ኢንቨስትመንት ለተሰማሩ ባለሀብቶች ብድር ተሰጥቷል፡፡ ብድር በሚሰጥበት ወቅት የአሰራር ግድፈቶች በመፈጸማቸው ከብድሮቹ ውስጥ የተወሰኑት ላይ ችግሩ ተከስቷል፡፡ ስለዚህ ችግሩን ለመፍታት አሰራሮችን መዘርጋትና ጥፋተኞችን ወደ ህግ የማቅረብ ስራ ይሰራል፡፡ በተከሰተው ችግር ልክ የሚመጥን እርምጃ የሚወሰድ ይሆናል፡፡

የተሰጡ ብድሮች እንዴት ይመለሱ በሚለው ላይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ዝርዝር ጥናት እያካሄደ ነው፡፡ በዚህ ጥናት መሰረት የማስመለሱ ስራ ይሰራል፡፡ ሆኖም በልማት ባንክ በአንድ ወቅት ላይ የተፈጸው ግድፈት በአጠቃላይ የባንኩን የተሟላ ገጽታ ያሳያል ብዬ አላምንም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ችግር በፈጠሩት ላይ እርምጃ ተወስዷል?
ዶክተር ስንታየሁ፡- እስካሁን የተሟላ እርምጃ አልተወሰደም፡፡ ግን ወደ እርምጃ ከመኬዱ በፊት በእጅ ላይ ያሉትን የተወሰኑ መረጃዎች ማጥራት ያስፈልጋል፡፡ ግድፈቱን ማነው የፈጸመው? መነሻ ዓላማው ምንድን ነው? የሚለው ከተጣራ በኋላ እርምጃው የሚወሰድ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የፋይናንስ ተቋማቱ ምን ያህል ትርፋማ ናቸው ?
ዶክተር ስንታየሁ፡- ከዓመት ዓመት እየጨመረነው፡፡ ትርፉ አንድ ነገር ሆኖ ግን በመንግስት የሚተዳደሩት የፋይናንስ ድርጅቶች ኢኮኖሚውን በምን ያህል አፋጥነውታል? የባንክን ተደራሽነትና ዘመናዊነትን አረጋግጠዋል? የሚለውም የስኬት መለኪያ መሆን አለበት፡፡ እነዚህ ሁለት የስኬት መለኪያዎች በገንዘብ ጠንካራ ካልተሆነ ሊመጡ አይችሉም፡፡ ስለዚህ በገንዘብ ረገድም ትርፋማ ናቸው ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከፋይናንስ ተቋማቱ ስኬት ጀርባ የኤጀንሲው ድርሻ አለ ማለት ይቻላል?
ዶክተር ስንታየሁ፡-የስኬት አባቱ ብዙ ነው፡፡ ከፋይናንስ ተቋማቱ ስኬት ጀርባ ኤጀንሲው አለ፡፡ውድቀትም ቢኖር ተጠያቂ ከሚሆኑት አንዱ ኤጀንሲው ነው፡፡ ስለዚህ ስኬቱ የሁላችንም ነው ብሎ መውሰድ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ያሉት የፋይናንስ ተቋማት ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ሲነፃፀሩ አቅማቸውም አገልግሎት አሰጣጣቸውም ደካማ መሆኑ ይነገራል፡፡ ይህን እንዴት ይገልፁታል?
ዶክተር ስንታየሁ፡- ሁሉም የፋይናንስ ተቋማት አሁን ባላቸው አቅም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸው ደካማ ነው ማለት ይቻላል፡፡እስካሁን የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት አይደለም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ የፋይናንስ ተቋማት አቅም በተሟላ መልኩ ጠንካራ አይደለም፡፡ በዚህ ሁኔታ የውጭ የፋይናንስ ኩባንያዎች ቢገቡ መወዳደር ይሳናቸዋል፡፡
አቅማቸው ከካፒታል መጠን ጋር ይያያዛል፡፡ ካፒታላቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ቢሆንም በተለይ በውጭ ምንዛሬ ክምችታቸው ከሌሎች አገሮች ባንኮች ጋር ሲወዳደሩ አነስተኛ ነው፡፡ የሰው ሀይላቸውና የአስተዳደር አቅማቸው ለውጥ እያመጣ ቢሆንም አሁንም ገና ይቀረዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም አዲስ የሚባል ቴክኖሎጂ መጠቀም ባይቻልም የተሻሉ የሚባሉትን መጠቀም ቢጀመርም በዚህ በኩልም የሚቀር አለ፡፡ እነዚህ ተደማምረው ሲታዩ ዕድገት ቢኖርም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸው ገና ይቀረዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ስትሆን፤ የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ከሆነ መንግስት ከፋይናንስ ዘርፉ እጁን ያወጣል?
ዶክተር ስንታየሁ፡- ኢህአዴግ የሚከተለው የልማታዊ መንግስት አቅጣጫ ነው፡፡ በዚህ መሰረት በተመረጡና ቁልፍ በሆኑ ዘርፎች ላይ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ይኖራል፡፡ መንግስት ጣልቃ የሚገባው ከሁለት መሰረታዊ ሀሳቦች በመነሳት ነው፡፡ አንደኛ የገበያ ጉድለት ባለባቸው ቦታ ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ ለኢኮኖሚው በጣም አስፈላጊ በሆኑና ሁሉንም ዘርፎች ሊያንቀሳቅሱ በሚችሉት ላይ ነው፡፡
ሆኖም መንግስት የግሉ ዘርፍ ይህን ለመሸፈን የሚችል አቅም መፍጠሩን ሲያረጋግጥ ከዘርፉ የሚወጣ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን መንግስት ከፋይናንስ ዘርፉ እጁን ያወጣል? ወይንስ በዚሁ ይቀጥላል? የሚለው ትልቅ የፖሊሲ ጉዳይ ስለሆነ በመንግስት ደረጃ ውይይት ተደርጎበት ወደፊት የሚወሰን ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን፡-የፋይናንስ ዘርፉ መሰረታዊ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?
ዶክተር ስንታየሁ፡- የፋይናንስ ዘርፉ የተሟላና ፍትሀዊ የሆነ የውድድር ቁመና ላይ መድረስ አለበት፡፡ሆኖም ውድድር በሚያደርጉበት ጊዜ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ባለቤትነቱ በጾታ፣ በብሄረሰብና በሌሎች ጉዳዮች የሚታጠር ከሆነ እንቅፋት ይፈጥራል፡፡ ምክንያቱም ቁጠባ የሚሰበሰብበት፣ ብድር የሚሰጥበት ቦታ በእነዚህ የመታጠር ዕድል ስለሚፈጥር ውድድርን ይገድባል፡፡ ውድድር መመራት ያለበት በጾታና በዘር ሳይሆን በገበያ መርህ ነው፡፡ ሆኖም የገበያ ውድድር ሳይሆን ባሌበትነት ብቻ የሚመዘንበት ከሆነ የአገር ኢኮኖሚን ይጎዳል፡፡ስለዚህ ውድድር በስራ አፈጻጸም፣ በአገልግሎት ዋጋ፣ በጥራትና በአይነት መመራት አለበት፡፡ እናም ውድድሩ በአገልግሎት፣በዋጋና በጥራት ከፍተኛ ደረጃ አለመድረሱ እንደ እንቅፋት የሚወሰድ ይሆናል፡፡
ሌላው ችግር የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት ዩኒቨሲቲዎቻችን ብዛት ያለው የሰው ኃይል እያፈሩ ናቸው፡፡ ሆኖም የባንክና የመድን ዘርፎች የሚፈልጉትን ባለሙያ በማፍራት ረገድ አሁንም ይቀራቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም የባለሙያዎች መነጣጠቅ ይታያል፡፡ ጠንካራ የሆኑ አሰራሮች አለመዘርጋትም በዘርፉ የሚስተዋል ተግዳሮት ነው፡፡ የሚፈለገውን ቴክኖሎጂ አለመታጠቅና ኅብረተሰቡ የፋይናንስ ግንዛቤ ማነስ በችግር ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ባንኮች በዘር፣ በሀይማኖትና በጾታ ላይ ተመስርተው የሚቋቋሙት ህጉ ክፍተት ስላለው ነው?
ዶክተር ስንታየሁ፡-በህግ ክፍተት አይደለም፡፡ ባንኮች ሲመሰሩቱ የሚከተሉት ህግ በብሄራዊ ባንክ ወጥቷል፡፡ ይህንን ህግ አሟልተው ነው የሚመሰረቱት፡፡ ነገር ግን ባንኮች ሲመሰረቱ የመጀመሪያውን የመመስረቻ ጽሑፍ የሚያዘጋጁ አካላት በዘር፣ በሀይማኖትና በጾታ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ይኖራቸው ይሆናል፡፡ ስለዚህ ‹‹የአክሲዮን ድርሻውን በዚህ አካባቢ ብንሸጥና ብንቀሳቀስ በአጭር ጊዜ ባንኩን ማቋቋምና ትርፋማ ማድረግ እንችላለን›› ከሚል ሀሳብ ሊሆን ይችላል ፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የግል ባንኮች ከስማቸው እንደምንረዳው የት አካባቢና በማን እንደተመሰረቱ አብዛኛው ህብረተሰብ በቀላሉ እንደሚያውቃቸው መረዳት አያዳግትም፡፡ ይህ ምን ጥቅምና ጉዳት አለው የሚለውን ማየት ይገባል፡፡ የፋይናንስ እንቅስቃሴ ገደብ የለሽ መሆን አለበት ፡፡
ምክንያቱም አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ እየገነባን ነው በምንልበት ወቅት ላይ የሰው ልጅ የፈለገበት ቦታ ሄዶ የመስራት መብቱ በተረጋገጠበት ጊዜ በዘር፣ በሀይማኖትና በጾታ ባንክን ማቋቋም ከገበያ መርህ ጋር የሚቃረን ነው፡፡ካፒታልም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ ትርፍ ማግኘት አለበት፡፡ ማህበረሰቡም መምረጥ ያለበት በሚሰጡት የአገልግሎት ዋጋ፣ ጥራትና አይነት እንጂ በባለቤቶቹ መሆን የለበትም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኤጀንሲው ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን ቢያስረዱን ?
ዶክተር ስንታየሁ፡- አንደኛው ጉዳይ የእነዚህን የፋይናንስ ተቋማት ተደራሽነትን ማረጋገጥ ነው፡፡የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ልማት ባንክና መድን ድርጀት አገልግሎቶችን ለሁሉም ህብረተሰብ ተደራሽ ማድረግ ዋና ዕቅድ ነው፡፡ ሶስቱም ተቋማት አገልግሎታቸውን በአጭር ርቀት ውስጥ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ መስጠት አለባቸው፡፡ አገልግሎቶቹ በተመጣጣኝ ዋጋና ቅልጥፍና እንዲሰጡ እንሰራለን፡፡ ይህን ማሳካት የቁጠባ አሰባሰቡ፣ ብድር የመስጠትና የክፍያ ስርዓቱ ዘመናዊ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ልማቱ እንዲፋጠን ያግዛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በጣም አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር ስንታየሁ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ጌትነት ምህረቴ

Published in ኢኮኖሚ

በእሥራኤልና በኢራን መካከል ያለው የቃላት ጦርነት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ወትሮም ቢሆን አንዳቸው ለሌላኛው የማይተኙት ሁለቱ አገራት በተያዘው ሳምንት መጀመሪያ የቃላት ጦርነታቸውን ከፍታ የሚጨምር ክስተት አስተናግደዋል፡፡ ይህ ደግሞ በሁለቱ አገራት መካከል እየከረረ የመጣው ጥላቻ በሠላም እጦት ለሚናጠው መካከለኛው ምሥራቅ ሌላ ሥጋት ሆኗል፡፡
ኢራን እአአ በ2015 ኒውክሌር የማምረት ተግባሯን ለማቆም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ከሆኑት አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ሩስያ፣ ፈረንሳይ ቻይናና ጀርመንን በተጨማሪነት ካካተተው ስድስት አገራት ጋር ተፈራርማ ነበር፡፡ ስምምነቱ ቴህራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯን ካቆመች አገራቱ ጥለውባት የነበረውን ማዕቀብ ለማንሳት መግባባት ላይ የተደረሰ ነበር፡፡
ሰኞ ዕለት ታዲያ እሥራኤል ኢራን ቃሏን ከመጠበቅ ይልቅ በድብቅ የኒውክሌር ልማቱን ገፍታበታለች የሚል ወቀሳ አቅርባለች። ይህንንም በተጨባጭ ሰነዶች ማረጋገጧን ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ የገለፁት፡፡ ሰነዱ ኢራን እአአ በ2015 የገባችውን ስምምነት በመጣስ የአቶሚክ መሣሪያዎችን በድብቅ እያመረተች እንደሆነ በግልፅ እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡
በእሥራኤል የደህንነት ኃይሎች አማካኝነት በእጃቸው የገባው ሰነድ ባለ 55 ሺ ገጽ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ገልጸዋል፡፡ ሰነዱ ቴህራን የኒውክሌር መርሀ ግብሯን ከመቀነስና ከማቆም ይልቅ ይበልጥ እንደገፋችበት በግልፅ እንደሚያሳይ በአገራቸው መከላከያ ሚኒስቴር ተቋም በመገኘት ባስተላለፉት መልዕክት አስታውቀዋል፡፡ ይህንን እውነታ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውቀውና እንዲረዳ አድርገዋል፡፡
«ከሰነዱ መረዳት እንደቻልነው ኢራን ዋሽታለች» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቴህራን በፀብ አጫሪነት ድርጊቷ መግፋቷን ዓለም ሊገነዘበው ይገባል ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ እአአ በ2012 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የኢራንን የኒውክሌር መርሀ ግብር የሚያሳይ ሰነድ ይዘው በመቅረብ የኢራንን «መስመር የለቀቀ ጉዞ» ያሉትን ትችት ሰንዝረው ነበር፡፡ ከስድስት ዓመት በኋላም ተመሳሳይ አቋም ማራመዳቸው የሁለቱ አገራት ፀብ እየከረረ በመምጣት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ሳይደርስ አይቀርም የሚሉ አሉ፡፡
እሥራኤል «በእጄ አስገባሁ» ያለችው ሰነድ ኢራን የኒውክሌር ማምረቻ የለኝም በማለት ዓለምን ለማታለል የምታደርገውን ጥረት በግልፅ የሚያሳይ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ አስታውቀዋል፡፡ እሥራኤል ሰነዱን «አጋሬ» ለምትላት አሜሪካ መስጠቷን ቢቢሲና ሮይተርስ ጽፈዋል፡፡ በቀጣይም ሰነዱን ለዓለም አቀፉ የኒውክሌር ኃይል ተቆጣጣሪ ተቋም እንደምትሰጥ ተናግራለች፡፡
የቴላቪቭን መግለጫ ተከትሎ ቴህራን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል የአፀፋ ምላሽ ሰጥታለች፡፡ የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃቫድ ዛሪፍ «የእሥራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ድርጊት የልጅ ጨዋታ የሚመስል ነው» የሚል ትችት በመሰንዘር የተባለው ውሸት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በውሸት መረጃ የኢራንን ስም ለማጠልሸት በእሥራኤል የተቀየሰ ስልት ነው ብለዋል፡፡
የእሥራኤል ውንጀላ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በግንቦት አጋማሽ ሀገራቸው «በስምምነቱ ትቀጥል ወይስ አትቀጥል በሚል ውሳኔ ለማሳለፍ በያዙት ዕቅድ ላይ ጫና ለማሳደር የተቀነባበረ የሕፃን ጨዋታ ነው» ስትል ኢራን አጣጥላዋለች።
አሜሪካ በበኩሏ ከእሥራኤል የተሰማው እውነት ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም ስትል ተደምጣለች፡፡ «የእሥራኤል የመረጃ ምንጭ ታማኝና ቀጥተኛ ነው» በማለትም ለተዓማኒነቱ ምስክርነቷን ሰጥታለች፡፡ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ «ከኢራን ጋር የተደረገው ስምምነት በውሸት ላይ የተመሰረተ ነው» በማለት ኢራን ከድርጊቷ ለመታቀብ ፍላጎት እንደሌላት ተናግረዋል፡፡
ከነጩ ቤተ መንግሥት የወጡትን መረጃዎች ዋቢ አድርጎ ቢቢሲ እንደዘገበው ስለ ኢራን ኒውክሌር ማምረት በእሥራኤል የቀረበው መረጃ አዲስ እና አሳማኝ ነው። የኢራንን ድብቅ እንቅስቃሴ በተጨባጭ ያሳያል፡፡ ሰነዶቹ አሜሪካ ከሰነደችው መረጃ ጋር የሚመሳሰል እና ቀጥተኛ ሲሆን ኢራን ከዜጎቿ እና ከመላው ዓለም ልትደብቀው እየሞከረች ያለውን ምስጪር ያጋለጠ ነው ብሏል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከእሥራኤል ጎን በመቆም ከኢራን ጋር የተደረገውን ስምምነት ለማቋረጥ የሚያስችል እርምጃ የመውሰድ አማራጭ ሚዛን እየደፋ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊት ግን ስምምነቱን የፈረሙት የአውሮፓ ሀገራት ችግሩን በአፋጣኝ እንዲፈቱት አሳስበዋል፡፡ ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን አሜሪካ ከኢራን ላይ ተነስቶ የነበረውን ማዕቀብ ወደ ማቋረጥ ትገባለች ብለዋል፡፡ በአባል አገራቱ አፋጣኝ መፍትሔ ካልተበጀለትም ስምምነቱ እአአ ከግንቦት 12 ቀን 2018 ጀምሮ ሊቋረጥ እንደሚችልም ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
እንግሊዝና ፈረንሳይ በበኩላቸው ከኢራን ጋር የተደረሰው ስምምነት እንዲቀጥል ፍላጎታቸውን አሳይተዋል፡፡ በተለይም እንግሊዝ ኢራን ስምምነቱን እንዳላፈረሰች በመጠቆም ይህን የሚያጠናክር በጣም ወሳኝ የሆኑ መረጃዎችን እያቀረበች መሆኗን እየገለጸች ነው፡፡
በእሥራኤልና በአሜሪካ የተያዘው የ«ቴህራን ስምምነቱን ጥሳለች» አቋም እአአ በ2015 በኦስትሪያ ቬና ላይ የተደረሰውንና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በፀደቀው የ2231 ስምምነት ላይ ውሃ ሊቸልስበት ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል፡፡
የሊባኖሱን ታጣቂ ቡድን ሂዝቦላን በመደገፍ በእሥራኤል ክፉኛ የምትተቸው ኢራን እአአ በ2011 የተቀሰቀሰው የሶርያ ግጭትን ተከትሎ ከፕሬዚዳንት በሽር አላሳድ ጎን በመቆም ንፁኃንን እየገደለች ነው የሚል ወቀሳ ይቀርብባታል፡፡
ኢራን የእሥራኤልን ሉዓላዊነት የሚዳፈሩ ጥቃቶችን ለመሰንዘር በድብቅ እየሰራች ነው ስትል ትከሳለች፡፡ ከዚህ ድርጊቷ ካልታቀበችም ከባድ ዋጋ ልትከፍል እንደምትችል እሥራኤል አስጠንቅቃለች፡፡
በአሸባሪዎች እየታመሰ ያለው መካከለኛው ምሥራቅ በእሥራኤልና ኢራን መካከል እየከረረ በመጣው ፀብ ለሌላ ቀውስ እንዳይዳረግ ስጋታቸውን የሚገልፁ አልጠፉም፡፡ አገራቱ ከመቀዛቀዝ መካረርን፣ ከመደራደር መፋጠጥን ምርጫቸው ማድረጋቸው ቀጣናው ከስጋት እንዳይወጣ ማድረጉ ነው የተመለከተው፡፡
ሁለቱ አገራት በክብ ጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየትና በመመካከር ችግራቸውን እንዲፈቱ ማድረጉ የተሻለና አዋጭ አማራጭ እንደሆነ በርካቶች ምክር ሃሳብ እየሰነዘሩ ነው፡፡ ለዚህም ከኢራን ጋር ስምምነቱን የፈረሙት አገራት በጉዳዩ ዙሪያ ጣልቃ ቢገቡ የተሻለ ውጤት ሊመጣ ይችላል ይላሉ፡፡
አሜሪካና የአውሮፓ ሀገራት ሁለት ፅንፍ ላይ ቆመው በኢራን ጉዳይ የተለያየ ሃሳብና አቋም ከማራመድ ይልቅ ወደ ሚያግባባ መስመር ለመምጣት በሚያስችል መስመር ቢሄዱ ሁሉንም ተጠቃሚ ሊያደርግ ይችላል ነው የተባለው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ሁለቱ አገራት ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን የሚፈጥሩት ግጭት ቀጣናውን ወደ ማይበርድ የሁከትና ብጥብጥ ዓለም ሊለውጠው ይችላል፡፡
ሁለቱ አገራት አሁን የደረሱበት የቃላት ጦርነት አፋጣኝ መፍትሔ ካላገኘ ችግሩ ወደ ወታደራዊ ጦርነት ሊያድግ እንደሚችል ሲ ኤን ኤን በዘገባው አመልክቷል፡፡ እአአ በ2015 እሥራኤል በኢራን እንደሚደገፍ በሚነገረውና በሶርያ እንደሚገኝ በሚገመተው የሂዝቦላ ታጣቂ ቡድን ላይ በሰነዘረችው የአየር ጥቃት የሒዝቦላ መስራች ልጅን ጨምሮ ስድስት አባላት መገደላቸውን አስታውሷል፡፡ ባለፈው የካቲት ወር እሥራኤል የአየር ክልሌን ጥሶ ገብቷል ያለችውን የኢራን ሄሊኮፕተር መጣሏን ዘገባው ያመለክታል፡፡ ይህም ኢራን በእሥራኤል ላይ ቂም እንድትይዝ አድርጓል፡፡
እነዚህ ሂደቶች የሁለቱ አገራት የቃላት ጦርነት ምናልባትም ጠመንጃ ወደ መማዘዝ ሊሄድ እንደሚችል የሚነገረውን ሃሳብ ሊያጠናክሩ ይችላሉ ነው የተባለው፡፡ የኢየሩሳሌምን የእሥራኤል ዋና መዲናነት በማፅደቅ አጋርነቷን ያጠናከረችው አሜሪካ ነገሩን ከማቀዝቀዝ ይልቅ ወደ ማጋጋሉ ብትሄድም ከኢራን ጋር በስምምነት የተጣመሩት እንግሊዝና ፈረንሳይ ከኢራን ጎን መቆማቸው ጉዳዩ በድርድር ሊፈታ ይችላል የሚል ተስፋ እንዲያዝ ማድረጉን ዘገባው አስታውቋል፡፡ መቋጫ ያጣው የቴላቪቭና የቴህራን ፍጥጫ አሁንም የቀጣናው ስጋት እንደሆነ ቀጥሏል፡፡

ዳንኤል ንጉሤ

Published in ዓለም አቀፍ
Wednesday, 02 May 2018 18:43

የመጀመሪያዎቹ 30 ቀናት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር መሪነቱን ከጨበጡ እነሆ ዛሬ 30 ቀናት ተቆጠሩ። ኢትዮጵያን ለምታክል ታላቅ አገር መሪ የትኩረት አቅጣጫቸውን ለመናገር እንኳን አንድ ወር ዓመትም ቢሆን አጭር ጊዜ ነው። የሙከራ ጊዜያቸውን ወይም የሥልጣን ቆይታቸውን በአንድ ወር ውስጥ መገምገም አይቻልም። የመንግሥት ሠራተኛ የሙከራ ጊዜ እንኳን 45 ቀን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመጋቢት 24 እስከ ሚያዝያ 24 በነበራቸው የሥራ ላይ ቆይታ ያደረጉትን እንቅስቃሴ በማየት ያለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት የሄዱባቸውን መንገዶች ስፋትና ርዝመት መዳሰስ ይቻላል።
የመጀመሪያ የሥልጣን ሽግግር የተከናወነው መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ነበር፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ለተመረጡ አዲስ ተሿሚ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማና የሕገ መንግሥቱን ሰነድ በማስረከብ ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግሩ ተበሰረ፡፡ በከፍተኛ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት፣ ሰብአዊ ፍቅርና መተቃቀፍ የተገለጠ የሥልጣን ሽግግር እንደነበር አይተናል፤ ሰምተናል። በዚሁ ዕለት የዶክተር አብይ አህመድን ንግግር አዳምጠናል። ግሩም ድንቅ ንግግር ነበር። በዚያ ንግግር ይዘት አቀራረብና አወራረድ ያልተደመመ ዜጋ የለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት የተናገሩትን አድንቀን ሳናበቃ በማግስቱ የመጀመሪያ ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ገብተው ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው፡፡ በማግስቱ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል አምቦ ከተማ ተገኙ፡፡ ከማርና ከወተት በሚጥም የንግግራቸው ይዘት የሕዝቡን ልብ ደስ አሰኙ፤ የወደፊት ዓላማቸውን ከወዲሁ አስቃኙ።
ከአምቦ ሲመለሱ የካቢኔ አባላቶቻቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው አፀደቁ። ካቢኔው በሦስት መልክ የቀረበ ነበር። አንደኛው ገጽታ ቀድሞ በነበራቸው ሥልጣንና የሥራ መደብ እንዲቀጥሉ የተደረጉ አመራሮች መኖራቸው ሲሆን፤ ሁለተኛው ከነበሩበት የሥራ መደብ ወደ ሌላ የሥራ ዘርፍ የተዛወሩትን ያካትታል፡፡ ሦስተኛው ገጽታ ደግሞ አዳዲሶቹን ተሿሚዎች ያካተተ ነው። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥሩ ውይይት አድርገውበታል። የመዋቅር ወይም የአደረጃጀት ጉዳዩን አስመልክቶ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት እና የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ሚኒስቴሮችን በአንድ ላይ አጣምሮ በአንድ ሚኒስትር እንዲተዳደሩ አድርጓል፡፡ ሁለቱን ግዙፍ የአገሪቱን የልማትና የዕድገት መሠረቶች በአንድ ላይ ማደራጀቱ የፋይናንስና የሰው ኃይል አቅምን ለማስተባበር፣ ዘርፉን ወደላቀ እመርታ ለማሸጋገር ያስችላል የሚለው ሃሣብ ብልጫ ስላገኘ ፀድቋል። ሌላው ብዙና ጥልቅ ውይይት የተደረገበት ጉዳይ በካቢኔው ውስጥ የሴቶች መጠን ማነስ ነው። አዎ! አንሷል! በእርግጥ ቀደም ሲል ከነበረው ቁጥር ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ ብልጫ አለው፡፡ በፊት ሦስት ሴቶች ብቻ የነበሩ ሲሆን አሁን ስድስት ሆነዋል። ይህ በካቢኔ ደረጃ ቢሆንም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ውስጥ ቢሆን የሴቶች ቁጥር በእጥፍ መጠን ለማሳደግ ለመጪው አጠቃላይ ምርጫ ዝግጅት ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል።
ሌላው የሕዝብ አስተያየት (አሉባልታ) ጭምጭምታ የሚባለው የተለመደው ሃሣብን የመለዋወጥ ዘዴ ነው፡፡ እገሌና እገሌ በአዲሱ ካቢኔ ውስጥ መካተት አልነበረባቸውም! የእገሌ ሚኒስቴር እገሌ ለተባለው ሚኒስትር መሰጠት አልነበረበትም! የእገሌ ብሔር ቁጥር በካቢኔ ውስጥ የለም ወይም አንሷል... የሚሉ ወሬዎች (አሉባልታ) በስፋት ሲናፈሱ ቆይተው አሁን ተንፍሰዋል፡፡ ወሬዎች በአብዛኛው በቀናነት መንፈስ ለአገሪቱ ከመቆርቆርና የአዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ጥረት ከማድነቅና ከማገዝ እሳቤ የመነጨ መልካም ሊባሉ የሚችሉ ዓይነት ናቸው፡፡
የካቢኔው ሹመት ግለሰቦችን ለመጥቅም ወይም ሕዝቦችን ለማበላለጥ የታለመ አለመሆኑ ለዜጎች ግልጽ ነው። ዓላማው በአገራችን ያለውን የመልካም አስተዳደር እጦት ሥርዓት ለማስያዝ፤ በአገሪቱ የተንሰራፋውንና የሕዝባችን ዋነኛ ጠላት የሆነውን ሥር የሰደደ ድህነት ለመቅረፍ፤ የዳበረ የዴሞክራሲ ባህል እንዲኖር ለማስቻል፤ የተደራጀ የሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመዝጋት መላው ሕዝብ አገሪቱ ከምታመነጨው ኢኮኖሚ ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔያቸውን አዋቅረውና አስፀድቀው ሲያበቁ የጀመሩትን የክልል የሥራ ጉብኝት ለማድረግና ከኅብረተሰቡ አባላት ጋር ለመወያየት በያዙት እቅድ መሠረት ወደ ትግራይ ክልል መቀሌ አምርተዋል። ከፍተኛ ክብር ያለው አቀባበል ተደርጐላቸው ለጀግኖች ሰማዕታት የአበባ ጉንጉን አኑረዋል፤ ከጦር ጉዳተኞች ጋር ተገናኝተዋል። ከሕዝቡ ጋርም ተወያይተዋል፤ ቀጥለውም በአዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽ ከ25 ሺህ በላይ ለሚሆኑ በተለይም ለወጣቶች ታላቅ ንግግር አድርገዋል። ወጣቱ ለእሳቸው ያለውን ክብርና ፍቅር በየንግግራቸው መሐል በከፍተኛ ጭብጨባና ዜማ አዳራሹ እስኪናጋ ድረስ ድጋፉን ገልጿል። በእውነቱ የሚገርም ነበር። እዚሁ አዲስ አበባ ሸራተን አዲስ ሆቴል ከአገሪቱ ባለሀብቶች ጋር ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡ ለባለሀብቶቹ ሚና እውቅና ሰጥተዋል። መንግሥት በማንኛውም መልኩ ባለሀብቶችን ማሳደድ ወይም ማሰር ወይም ሀብት የማፍራት እንቅስቃሴዎቻቸውን ማስተጓጎል እንደማይፈልግ አረጋግጠውላቸዋል። ከባለሀብቱ የሚጠበቀው ሥራ ሕግን በተከተለ አግባብ በተገቢው አካሄድ መንቀሳቀስ ብቻ ነው። በዱባይና በቻይና የተከማቸውን የውጭ ምንዛሬ ወደ አገር ቤት በመመለስ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ችግር ለማቃለል እንዲንቀሳቀስ አሳስበዋል፡፡ ባለሀብቱ በከፍተኛ ጭብጨባ ለማሳሰቢያው ያለውን ድጋፍ ገልጿል። አንጀቱ ቅቤ ጠጥቷል ማለት ይቻላል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጣይ የሥራ ጉብኝት በአማራ ክልል በጎንደርና ባህርዳር ከተሞች ነበር፡፡ ጎንደር ሲገቡ የአፄ ቴዎድሮስ መገለጫ የሆነውን ጃኖ ለብሰው አምረውና ደምቀው ታይተዋል፡፡ እንደለመደው የሁሉም ክልል መሪዎች እንዳደረጉት ሁሉ የአማራ ክልል መስተዳድር ኃላፊዎች ታላቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ የአጼ ፋሲል ግንብ ምስል ያለበት ሽልማት ሰጥተዋቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎንደርና በባህር ዳር ያደረጉት ንግግር እጅግ በጣም የልብ የሚያደርስ ነበር። «ካጠፉሁ ቆንጥጡኝ... የገበሬ ልጅ ነኝ» ብለዋል። ከዚህ በላይ ንግግር ከወዴት ይመጣል? ግርማዊ ጃንሆይ በረጅሙ የንግሥና ዘመናቸው አንድ ጊዜ «ልጃችሁ ነኝና ሳጠፋ ቅጡኝ» ያሉበት አጋጣሚ ስለመኖሩ አናውቅም፡፡ ደርግም እንኳን ቆንጥጡኝ ሊል ቀርቶ በማንኛውም በጥይት ከመለጠጥ አይመለስልም «እኔ ብቻ ነኝ ልክ» በሚል ተቃዋሚዎቹን ብቻ ሳይሆን ከእሱ የተለያዩ ሃሣብ ያላቸው ጀሌዎቹን ሳይቀር የተለያየ ስም (ታፔላ) እየሰጠ ፍትሐዊነትን በሚነፍግ አስተዳደር ውስጥ ያለፈ ሕዝብ ይህን የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን ንግግር ሲሰማ ምን ያህል ደስታ እንደሚሰማው መገመት ያዳግታል።
በእስካሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአንድ ወር ጉዞ ከተሰሩ ታሪካዊ ክንውኖች በሕዝብም ዘንድ በአድናቆት የሚነሳው ማክሰኞ ሚያዝያ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በታላቁ ቤተመንግሥት ለቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የተደረገው የክብር ሽኝት የእራት ግብዣ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአቶ ኃይለ ማርያምና ለባለቤታቸው ሽልማትና የምስክር ወረቀት ሰጥተዋል። ታላቅ ንግግርም አድርገዋል። «አቶ ኃይለማርያም በንጹህ ከሚነገሩትና በምሳሌነት ከሚታዩት መሪዎች አንዱ ናቸው፤ ከሁሉም በላይ እጃቸው ንፁህ የሆኑ ሌብነት የሚፀየፉ ለሁላችንም አርአያ መሆን የሚችሉ፣ በመስራትና በመልፋት ብቻ ማገልገል እንደሚቻል ለብዙዎቻችን ያስተማሩ፣ ንጽህናቸውን እሳቸውና ቤተሰባቸው ብቻ ሳይሆኑ የሥራ ባልደረቦቻቸውና ጓደኞቻቸው ይመሰክሩ ላቸዋል፡፡ አስቸጋሪና ፈታኝ በሆነ የሌብነት ልምምድ ውስጥ ባለንበት በዚህ ዘመን በንጽህና ከሚነገሩ ምሳሌዎች አንዱ በመሆናቸው እንደ ሀገርም እንደ አፍሪካም ኩራት የሆነ ባህርይና ራስን የማሸነፍ ብቃትም ያላቸው ስለሆኑ ክብር ይገባቸዋል» ሲሉ በእውነተኛ ስሜትና ከልብ በመነጨ ምርጥ ንግግር አወድሰዋቸዋል።
በዚሁ የክብር ሽንት ፕሮግራም ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ስለ ተሰጣቸው ክብርና ሽልማት ስለተደረገላቸው መንግሥታዊ ሽኝት አመስግነው በሥልጣን ላይ ሳሉ ካሳለፉት ልምድና እውቀት በመነሳት ሕዝቡ ለአዲሱ አመራር በትዕግስት ጊዜ እንዲሰጣቸው አሳስበዋል። «የተሰጣቸው ሀገርን የመምራት ኃላፊነት እጅግ ከባድና ግዙፍ በመሆኑ ሁሉንም ችግር በአንድ አፍታ እንዲፈቱለት ሕዝቡ ተዓምር መጠበቅ የለበትም፤ ከአዲሱ አመራር ጎን በመቆም ሁላችንም የየራሳችንን ድርሻ እንወጣ፣ ሥልጣን ማለት ሕዝብን ማገልገያ እንጂ ምንም ማለት አይደለም» በማለት «ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጋር አብሮ ለመሥራት እንትጋ» ብለዋል። «በአገሪቱ የተፈጠረውን ይህንን አመቺ ሁኔታ በአግባቡ ሳንጠቀምበት ቀርተን አንዴ ከእጃችን አፈትልኮ ከወጣ ዳግመኛ ለመመለስ ወደማይቻል አዘቅት ውስጥ እንገባለን፣ ሥራው ወገብ የሚያጐብጥ ነው፤ ችግራችን ብዙና ሰፊ ነው። ስለዚህ ከአመራሩ ጋር አብረን እንስራ፤ ትዕግስት ይኑረን፤ ጊዜ እንስጥ …» ሲሉ ተደምጧል፡፡ ሕዝቡም ለአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በተሰጠው ክብር በጣም ረክቷል። እንዲህ ዓይነት የክብር አሸኛኘት ለሌሎች አገራት በተለይም ለአፍሪካ ትልቅ ትምህርት ነው፡፡ በእኛ የታየው ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ለብዙ የዓለም አገሮች ትምህርትና አርአያ የሚሆን ነው።
ሌላው የወሩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እንቅስቃሴ ሐሙስ ሚያዝያ 18 ቀን 2010 ዓ.ም ለሥራ ጉብኝት የታላቋ ኢትዮጵያ ተምሳሌት በሆነችው፣ ሕዝቦች ተፋቅረውና ተከባብረው በሚኖሩባት በጥንታዊ ታሪኳና ባህሏ ከምትታወቀው የደቡብ ክልል ዋና ከተማ በሃዋሳ መገኘታቸው ነው፡፡ በዚያም ሕዝቡ ታላቅና ደማቅ አቀባበል አድርጐ ላቸዋል፡፡ እሳቸውም ሕዝቡን የማረከና ያረካ መልዕክት አስተላልፈዋል። በእነዚህ 30 ቀናት ውስጥ የተለመዱት የዕለት ተዕለት ሥራዎች አሉ። የተመድን የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኃላፊንና የአሜሪካውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ ዶናልድ ያማማቶን አነጋግረዋል፡፡ አገሪቱ ያከናወነችውን ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር፤ ቀጣይ የልማትና የዴሞክራሲ ሥራዎችና የሰብአዊ መብትና አያያዝን በተመለከተ ገለፃና ማብራሪያ አድርገውላቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ወደ መሪነት ከመጡ ከሀገር ውጪ የመጀመሪያቸው የሆነውን የሥራ ጉብኝት በጅቡቲ አድርገዋል፡፡ በጅቡቲ የሁለት ቀናት ጉብኝት የሁለቱን አገራት የኢኮኖሚ ውህደት የሚፈጥሩ ስምምነቶችን በማከናወን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ እነዚህንና ሌሎችንም የመሪ ተግባራት በማከናወን ፋታ በሌለው ሁኔታ የመጀመሪያዎቹን 30 ቀናት የሥራ ላይ ቆይታ በሚደንቅ ሁኔታ አጠናቀዋል፡፡

ግርማ ለማ

 

Published in አጀንዳ

  በታሪካዊው መጋቢት 24 ቀን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተከናወነው ታሪካዊ የሥልጣን ሽግግር እነሆ ዛሬ አንድ ወር ሞላው፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተበሰረበት ሰባተኛ ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቃለ መሃላ ፈፀሙ፡፡ ለሌሎች በአርዓያነት የሚጠቀስ ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግርም በህዝብ እንደራሴዎቹ ፊት ተፈፀመ፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣንን ለተተኪያቸው ፍጹም በሆነ ኢትዮጵያዊ ፍቅርና አክብሮት አስረከቡ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ ለህገ መንግስቱ ታማኝ በመሆን ከሀገሪቱ እና ከህዝቡ የተጣለባቸውን ሃላፊነት በቅንነት፣ በታታሪነት፤ እንዲሁም ህግና ሥርዓቱን መሰረት በማድረግ ስራቸውን ለመፈፀም ቃለ መሀላ ፈጸሙ፡፡ የተረከቡትን ህዝባዊ አደራ በብቃትና በቁርጠኝነት ለመወጣትም ቃል ገቡ፡፡ ይህን ተከትሎም በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋት ወደ ቀደመው ሠላም ለመመለስ ከህዝቡ ጋር መወያየትን የመጀመሪያ ሥራቸው አደረጉ፡፡ በዚህም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በመዘዋወር ከህዝቡ ጋር መከሩ፣ የመንግስትን አቅጣጫዎች አስረዱ፡፡ ከህዝብ የሚጠበቀውንም ግልጽ አደረጉ! ከህዝቡ ለተነሱ ጥያቄዎችም ተገቢውን ምላሽና ማብራሪያ ሰጡ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሥልጣን ዘመን መገደብን ጨምሮ የተለያዩ የህግ ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ ቃል ገቡ፡፡
በተለያዩ መድረኮችም ከተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ከባለሀብቶች፣ ከወጣቶችና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመገናኘት የአገሪቱን ሠላም ለማረጋገጥና ልማትን ለማስቀጠል በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙርያ ተወያይተዋል፡፡ የማይታለፍ ቀይ መስመር በማስመርም የአዲስ ምዕራፍ ጉዞውን ወደ ፊት ለማራመድና ለማፋጠን ያስችላሉ ያሏቸውን አመራሮች በመምረጥ ካቢኔያቸውን አዋቅረው በምክር ቤት አስፀድቀዋል፡፡ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት በግልፅነትና በተጠያቂነት አሰራር እንደሚፈጸሙም አስረድተዋል፡፡
በጣና ፎረም አማካኝነት ከተለያዩ የአፍሪካ መሪዎች ጋር ካደረጉት የጎንዮሽ ውይይት በተጨማሪ ከአገር ውጭ የመጀመሪያቸው በሆነው የጅቡቲ ጉብኝት ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነትና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር አምባሳደር ዶናልድ ያማሞቶና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኃላፊን ጨምሮ የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶችን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡ በዚህም ተገቢውን የዲፕሎማሲ ሥራ አከናውነዋል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ አክብሮትና ትህትና የሰፈነበት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር የክብር ሽኝትም ሌላው የወሩ አስደማሚ ሥነ ሥርዓት ነበር፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ላገለገሉበት ምስጋና ተችሯቸው በክብር ተሸኝተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ30 ቀናት ያከናወኗቸው ተግባራት በድምር ሲታዩ ስኬታማና ለቀጣይ ስራዎች ምቹ መደላድል የፈጠሩ ነበሩ ለማለት ያስደፍራል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወን ችለዋል፡፡ በተለይም ለሁሉም ነገር መሰረት የሆነውን ሠላምን ለማረጋገጥ የተጓዙበት መንገድ መልካም ፍሬን እንደሚያፈራ ጅምሮች ታይተዋል፡፡ የሠላሙ ባለቤትና ተጠቃሚ የሆነው ህዝብ ለሠላም ዘብ እንዲቆም ከህዝቡ ጋር በቅርበት በመገናኘት ያደረጉት ውይይት ጥሩ ውጤት እንደሚመጣም እምነት አሳድሯል፡፡ ህዝቡም የሚጠበቅበትን በመፈጸም የአገሪቱ ሠላም እንዳይደፈርስ ከመንግስት ጎን በመቆም የበኩሉን እንደሚወጣ ቃል በመግባት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሠላም ጥሪ ድጋፉን ሰጥቷል፡፡ ለሠላም መረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚንቀሳቀስና በንቃት እንደሚሳተፍም አረጋግጧል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ በስኬት የታጀበ ጉዞ በቀጣይም ግለቱን ጠብቆ ሊጓዝ ግድ ይላል፡፡ ሠላምን መሰረት ያደረገው የልማት እንቅስቃሴ ይበልጥ መጠናከር አለበት፡፡ በችግሮችና መፍትሔዎች ላይ በመወያየት የተፈጠረው የጋራ መግባባት በተግባራዊ ሂደቱ ላይ መንጸባረቅ አለበት፡፡ አሁን ጊዜው የስራ ነው፤ ተግባራዊ ሥራ እውን የሚሆንበት፡፡ቃሉን ወደ ተግባር በማውረዱ ሂደት የሁሉም ርብርብና ተሳትፎ በጣም ወሳኝ ነው፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በየመድረኮቹ የተነሱት ሃሳቦች ሥጋ ለብሰው ወደ መሬት እዲወርዱና ውጤታማ እንዲሆኑ መንግስትም እንደመንግስት ህዝቡም እንደ ህዝብ ሁሉም የድርሻውን መውሰድና መወጣት ይኖርበታል፡፡ ችግሮችን በማስወገዱና መልካም የሆኑትን ጅምሮች በማጠናከሩ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጨባጭ ተሳትፎ መታየት አለበት፡፡ ይህን ማድረግ ከተቻለ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወርሃዊ ስኬት በቀጣዮቹ ወራትም በስኬት መታጀቡ አይቀሬ ይሆናል፡፡ የመሪ ስኬት የአገርና የህዝብ ስኬት ነው፡፡ ህዝብና አገር በመሪ ይወከላሉና፡፡
መንግስትና ህዝብ ተባብረውና ተናበው ከተጓዙ የማይታለፍ ችግር፣ቨየማይፈነቀል ድንጋይ፣ የማይናድ ተራራ፣ የማይመዘገብ ውጤት፣ የማይመጣ ለውጥ አይኖርም፡፡ እናም መጪውን ጊዜ በስኬት ለማጀብ ፖለቲከኛው፣ የሃይማኖት መሪው፣ ምሁሩ፣ ወጣቱ፣ ባለሀብቱ፣ ዳያስፖራውና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የበኩሉን መወጣት ይጠበቅበታል፡፡ ይህን ማድረግ ከተቻለ በዚህ ወር የታየው ስኬት አድማሱን እያሰፋና ጉልበቱን እያበረታ በቀጣዮቹ ወራት መደገሙና የምንናፍቀው አስተማማኝ ሰላምና ብልጽግና እውን እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡ በስኬት የታጀበው ወር በውጤታማ አመት እየተተካ የሚፈለገውን ግብ መምታትና ዓላማን ማሳካት ይቻላል፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

ወቅቱ በአገሪቱ አብዛኛው ክፍል መሰረተ ልማት ያልተስፋፋበት ጊዜ ነበር፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎት ከተማ ቀመስ በሆኑ አካባቢዎች ወደ ዘመናዊነት ለመሻገር ገና ዳዴ እያለ ነው። ከ50 ዓመት በፊት ይህ እውነታ ነበር፡፡ ከገጠርነት ባልተሻገሩት አካባቢዎች መንገድ አለመኖሩ የሰዎችን እንቅስቃሴ አድካሚ እና አሰልቺ አድርጎታል። መንገድ በሌለበት ህመምተኞችን ወደ ሆስፒታል ማድረስ እጅግ አስቸጋሪ ነው። የጉራጌ ዞን ህዝብም ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ ለማሳለፍ ተገዷል፡፡

በሥራ ፈጣሪነቱና አክባሪነቱ፣ ለተሻለ ህይወትና ለውጥ በትጋቱ የሚታወቀውና በጽናቱ በአርዓያነት የሚጠቀሰው የጉራጌ ህዝብ የዚሁ ችግር ሰለባ ሆኖ ቆይቷል። የጉራጌ ህዝብ ከጥንት አባቶቹ ጀምሮ ማንም ለልማት መደራጀት ባልጀመረበት ወቅት ከችግር ለመውጣት በራስ አቅም ተደራጅቶ መንገድ መስራት ጀመረ፡፡ በዚህም አካባቢውን በማልማት አርአያነቱን አሳየ።
መንገድ ያልተዘረጉባቸው አካባቢዎች ዛሬ የመንገድ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ የእርምጃው አሃዱ ከትናንት እስከ ዛሬ ዘልቆ የተባበረ ክንዱን በማጠናከር በሌሎች መሰረተ ልማቶች ላይም ታየ። በዚህ ጉዞ የተሳተፉትን የጉራጌ ልማትና ባህል እና የጉራጌ ዞን ልማት ማህበራትን በማካተት የልማት ጉዞው ቀጠለ፡፡
የጉራጌ ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግና ባህሉን ለመጠበቅ በሚንቀሳቀሱ ማህበራት የተለያዩ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን የቡታጅራ ከተማ ነዋሪ ወጣት ጸጋዬ ወርቁ ይገልፃል፡፡ ለአብነትም በጉራጌ ልማት ማህበር አማካኝነት የተቋቋመው ጉዞ አውቶኬር ኢንጂነሪንግ ማዕከል በዞኑ ለሚገኙ ተሽከርካሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ የጥገና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቅሷል፡፡ የልማት ሥራዎቹ ለወጣቱም የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ነው የሚያስታውሰው፡፡
የቡታጅራ ከተማ ነዋሪ ወጣት ትዕግስት አመልጋ ማህበራቱ የማህበረሰቡን ባህላዊ እሴቶች ለማሳደግ የተለያዩ ልማቶች እንደሚያካሂዱ ጠቁማ፣ ይህ ግን አጥጋቢና የተደራጀ አይደለም ትላለች፡፡ የዚህ መንስኤም ከማህበራቱ የተናጠል እንቅስቃሴ የሚመነጭ ሊሆን እንደሚችል ትናገራለች፡፡ ማህበራቱ በተናጠል መጓዛቸው የተደራጀና ቀጣይነት ያለው ሥራ እንዳይካሄድ ሳያደርገው አይቀርም ብላለች፡፡ በጉራጌ ተወላጆች የተቋቋሙት ማህበራት ከ50 ዓመት በላይ ዕድሜ ቢያስቆጥሩም በተናጠል መንቀሳቀሳቸው የዕድሜያቸውን ያህል ውጤታማ እንዳላደረጋቸው ገልፃለች፡፡ ‹‹በህብረት ቢንቀሳቀሱ ከዚህ በላይ ውጤት ማስመዝገብ ይችላሉ›› የሚል እምነት አላት፡፡
የአካባቢው የአገር ሽማግሌ አቶ አለማየሁ ጠንክር በበኩላቸው ማህበራቱ በጉራጌ ዞን ለሚያከናውኑት የልማት ሥራዎች ህብረተሰቡ የበኩሉን ተሳትፎ ማድረጉን ያመለክታሉ፡፡ ሆኖም ግን የህብረተሰቡ ድጋፍ በቀጣይ በደንብ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡ ስለሆነም የልማት ሥራዎቹን ለማስፋፋት ህብረተሰቡ በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የጉራጌ ህዝብን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግና ባህሉን ለመጠበቅ በሚንቀሳቀሱ ማህበራት የወልቂጤና ቡታጅራ ከተማን ጨምሮ በዞኑ 11 ወረዳዎችን ያካለሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ መደረጋቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከፕሮጀክቶቹ መካከል ትምህርት፣ ጤና ጣቢያ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ ግብርናና የመንገድ ልማት ይገኙበታል፡፡
ከጉራጌ ልማት ማህበር በተጨማሪ የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበርን የመሳሰሉ ማህበራት ለዞኑ ዕድገትና ለህዝቡ ተጠቃሚነት መስራታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ቡኢ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ፣ የአገና እና የሀዋሪያት ከተማ ሴት ተማሪዎች ማደሪያ ሆስቴሎች፣ የጉመር ወረዳ የውሃ ፕሮጀክት፤ የጌታ፣ የቸሃ፣ የመስቃን፣ የእነሞርና ኤነር እንዲሁም የእንደጋኝ ወረዳዎች የትምህርት ተቋማት ግንባታዎች፤ የወልቂጤ ጠቅላላ ሆስፒታል በማህበራቱ አማካኝነት የተገነቡና እየተገነቡ ያሉ የልማት ሥራዎች መሆናቸውን መረጃው ያትታል፡፡
የጉራጌ ብሄረሰብን የልማትና የባህል እሴቶችን ለማሳደግ የተጀመረው እንቅስቃሴ ረጅም ጊዜ ቢሆነውም ውጤታማነቱ ያን ያህል መሆኑን በጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር የቋንቋና ባህል መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ጌታቸው ዳዊ ይናገራሉ፡፡ የማህበራቱን የተናጠል ጉዞ፤ወደ አንድነት ለማምጣት ፍላጎቱና ምኞቱ ቢኖርም መፍትሄ ሳያገኝ መቆየቱን አመልክተዋል፡፡
ከሳምንት በፊት በጉራጌ ዞን በቡታጅራ ባህል ማዕከል የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር እና የጉራጌ ዞን ልማት ማህበር ይፋዊ ውህደት ፈጥረዋል። «ጠንካራ አንድነት ለላቀ ሁለንተናዊ ልማት» በሚል መሪ ቃል በተፈጸመው ጥምረት ማህበራቱ ከተናጥል ጉዞ ወደ አንድነት መምጣታቸውን በይፋ አውጀዋል፡፡
በዞኑ ውስጥ የልማትና የባህል ግንባታዎችን የሚያከናውኑ ማህበራት ወደ አንድ መምጣታቸው ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ዶክተር ጌታቸው ይናገራሉ፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት የጉራጌ ልማት ማህበር እና ባህል ማህበር መዋሀዳቸው ሌሎች ማህበራትም ወደ አንድ እንዲመጡ በር መክፈቱን አስታውሰዋል፡፡ ሁለቱ ማህበራት በተወሰኑ አካባቢዎችና ልማቶች ላይ ብቻ የሰጡትን ትኩረት አንድነታቸውን በማጠናከር የተደራጀ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚችሉ ነው የጠቆሙት፡፡
የቡታጅራ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ማርቆስ ማህበራቱ መዋሃዳቸው በተሻለ አቅም የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በስፋት እንዲያከናውኑ እንደሚረ ዳቸው ይናገራሉ፡፡ ማህበራቱ ቀደም ሲል ከነበሩበት የተናጠል ጉዞ አቅማቸውን በማጠናከር የተሻለ ልማት ለማከናወንና ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚጠቅም ነው የገለፁት፡፡
የኢፌዴሪ ወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ርስቱ ይርዳው ውጭ አገር የሚኖሩ የብሄረሰቡ ተወላጆች መንግሥትና ህዝብ የሚያደርጉትን ርብርብ ማጠናከር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ዳያሳፖራዎቹ ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ነው ያሳሰቡት፡፡ ለዞኑ ልማት መጠናከር የማህበራቱ ውህደት ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል ብለዋል፡፡ በየደረጃው የሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች በማህበራት አማካኝነት የሚያደ ርጉትን የልማት እንቅስቃሴ መደገፍ ይኖርባቸዋል።

ዜና ሐተታ
ዳንኤል ዘነበ

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።