Items filtered by date: Thursday, 03 May 2018
Thursday, 03 May 2018 16:58

የሜይ ዴይ ቻምፒዮኖች

በአገራችን ለ43ኛ በዓለም ደግሞ ለ129ኛ ጊዜ የተከበረውን የሠራተኞች ቀን (ሜይ ዴይ) አስመልክቶ በሠራተኛው የስፖርት ማህበራት መካከል በተለያዩ ስፖርቶች ጨዋታዎች ተካሂዶ መቖለ ከተማ ላይ ፍፃሜ አግኝተዋል። አዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የሠራተኛ ስፖርት ለአንድ ወር ያህል የጥሎ ማለፍ ውድድሮችን አከናውነዋል። በተመሳሳይ ከመቖለ ከተማ ያሉት የሠራተኛ ስፖርት ማህበራት የጥሎ ማለፍ ውድድራቸውን አድርገው ማሸነፍ የቻሉት በፍፃሜ ውድድሮች ከአዲስ አበባ አሸናፊዎች ጋር ለፍፃሜ ተገናኝተዋል።
በሠራተኛው የስፖርት ውድድር ከፍተኛ ትኩረት በሚሰጠው የእግር ኳስ ጨዋታ የአዲስ አበባው የጥሎ ማለፍ አሸናፊ አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ የመቖለ ከተማውን ማ ጋርመንት በሜዳውና በደጋፊው ፊት በማሸነፍ የሜይ ዴይ ቻምፒዮን መሆን ችሏል። አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ጨዋታውን ያሸነፈው በመለያ ምት ሰባት ለስድስት መሆኑን የኢሠማኮ የስፖርት ክፍል ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ካሳ ያደረሱን መረጃ ያመለክታል።
በጥሎ ማለፍ ውድድሮች ጠንካራ ፉክክር ሲያስተናግዱ ከቆዩ ውድድሮች አንዱ ቮሊቦል ነው። በዚህ ውድድር በሁለቱም ፆታ በተደረጉ የፍፃሜ ጨዋታዎች የአዲስ አበባ የስፖርት ማህበራት ቻምፒዮን መሆናቸው ታውቋል። በሴቶች አንበሳ የከተማ አውቶብስ ማ ጋርመንትን ሁለት ለዜሮ በሆነ ውጤት በመርታት ቻምፒዮን ሲሆን በወንዶች አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግን ሦስት ለዜሮ ማሸነፍ ችሏል።
አዝናኝ በሆነው የገመድ ጉተታ ውድድር በሴቶች ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት መሰቦ ሲሚንቶን ሁለት ለምንም በመርታት ቻምፒዮን መሆኑን አረጋግ ጧል። በወንዶች ተመሳሳይ ውድድርም ብርሃንና ሰላም መስፍን ኢንዱስትሪያልን ሁለት ለአንድ በመርታት በአንድ ስፖርት ሁለት ዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።
የመቖለ ከተማ በዳርት ውድድር የሚሳተፍ ማህበር አለማቅረቡን ተከትሎ በፍፃሜ የተገናኙት ሁለት የአዲስ አበባ ማህበራት ነበሩ። በዚህም መሰረት በወንዶች ስብሃቱና ልጆቹ በኢትዮ ቴሌኮም ሁለት ለዜሮ ተሸንፏል። በሴቶች ደግሞ ብርሃንና ሰላም አንበሳ አውቶብስን በተመሳሳይ ውጤት ረቶ ዋንጫውን አንስቷል። በዳማ ጨዋታ አንበሳ አውቶብስ አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽን ሦስት ለሁለት በመርታት ቻምፒዮን ሲሆን፣ በገበጣ ጨዋታ ጂኦሴንቴቲክ ኢንዱስትሪያል በተመሳሳይ አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽን ሁለት ለአንድ በመርታት ዋንጫውን ወስዷል። በከረንቦላ ውድድር ብርሃንና ሰላም ማተሚያ አዲግራት መድኃኒት ፋብሪካን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ የሰበሰበውን የዋንጫ ቁጥር አራት አድርሷል። በቼስ ውድድር ኢትዮ ቴሌኮም መሰቦ ሲሚንቶን ሁለት ለዜሮ በመርታት ማሸነፉም ታውቋል።
በሁለቱም ፆታ በተደረገው የጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር በሴቶች አንበሳ አውቶብስ ኢትዮ ቴሌኮምን ሦስት ለሁለት ማሸነፍ ሲችል በወንዶች ኢትዮ ቴሌኮም መሰቦ ሲሚንቶን በተመሳሳይ ውጤት አሸንፎ አካክሷል። እንደ አጠቃላይ አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ በበርካታ ውድድሮች ላይ ለፍፃሜ መድረስ ቢችልም ዋንጫ ማንሳት የቻለው በሁለቱ ብቻ ነው። ብርሃንና ሰላም ማተሚያ አራት ዋንጫዎችን በማንሳት ቀዳሚ በሆነበት ውድድር አንበሳ አውቶብስ ሦስት ዋንጫዎችን ወስዷል።
በውድድሮች የነበሩትን ጠቅላላ ዋንጫዎች የአዲስ አበባ የሠራተኛ ስፖርት ማህበራት ጠራርገው ቢወስዱም የመቖለ ከተማ የሠራተኛ ስፖርት ማህበራት ሌሎች ዋንጫዎች ተበርክቶላቸዋል። መሰቦ ሲሚንቶ በበርካታ ስፖርቶች ተሳታፊ በመሆን ዋንጫ ሲበረከትለት በሴቶች ጥሩ ተሳታፊ በመሆን ማ ጋርመንት ዋንጫ ተሸልሟል። ማ ጋርመንት በተመሳሳይ የፀባይ ዋንጫ ተሸላሚም ነው።

 

ፌዴሬሽኖች ለአፍሪካና ለዓለም ወጣቶች  ጨዋታ እየተዘጋጁ ነው

 

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሦስተኛውን የአፍሪካና የዓለም ወጣቶች ጨዋታ ዝግጅት አስመልክቶ ከብሄራዊ ፌዴሬሽኖች ጋር ምክክር ማድረጉን ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ አሳውቋል። በመድረኩ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ለጨዋታዎቹ ዝግጅት መጀመራቸውን አሳውቀዋል።
ኮሚቴው በዋናው ጽህፈት ቤት አዳራሽ ከብሄራዊ ፌዴሬሽኖች ጋር ከቀናት በፊት ባደረገው ውይይት በቀጣይ በሚካሄዱት 3ኛው የአፍሪካና የዓለም ወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታ ውጤት ለማስመዝገብ በእቅድ፤ ዝግጅትና ተሳትፎን በተመለከተ በጥልቀት ተወያይቷል።


የውይይት መድረኩን የመሩት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ፤ የውይይት መድረኩ አላማ ኢትዮጵያ በቀጣይ በሦስተኛው የአፍሪካና የዓለም ወጣቶች ጨዋታ ተሳታፊ ስትሆን ህዝብና መንግሥት የሚጠብቁትን ውጤት ለማምጣት ካሁኑ በቂ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ፣ ለእነዚህ ጨዋታዎች ብሄራዊ ፌዴሬሽኖች በተጨባጭ ምን ዝግጅት እያደረጉ እንዳለ ለማወቅ በማሰብ ነው።
በዚህም በዝግጅት ወቅት ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ያጋጠማቸውን ተግዳሮቶች በማንሳት ለመፍትሄው በጋራ ለመረባረብ፣ ከኮሚቴው ጋር ተናበውና ተደጋግፈው ለመስራት እንደሚያግዛቸው ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል። ከዚህ ጎን ለጎንም «ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የኦሊምፒክ ኮሚቴውን እቅድ መነሻ በማድረግ ለሁለቱ ጨዋታዎች የራሳቸውን እቅድ በማዘጋጀት እንዲሰሩ ያግዛቸዋል» ብለዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት ብሄራዊ ፌዴሬሽኖች አትሌቲክስ፣ ብስክሌት፣ ቦክስ፣ ውሃ ዋና እንዲሁም ሌሎችም ማህበራት በአጠቃላይ እያደረጉ ስላለው ዝግጅት፣ የማጣሪያ ውድድሮችና ውጤቶቻቸው እያዘጋጇቸው ስላሉ ስፖርተኞች እንዲሁም ስለገጠማቸው ችግሮችና ሌሎችም ጉዳዮች አንስተው ውይይት አድርገዋል።
ማህበራቱ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት፤ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ከምንጊዜም በተሻለ ሁኔታ ለብሄራዊ ፌዴሬሽኖች ልዩ ትኩረት በመስጠት በሁሉም መስክ እያደረገ ያለው ድጋፍና ክትትል የሚያስመሰግነው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የበኩላ ቸውንም ለመወጣት ኮሚቴው ለሁለቱ ጨዋታዎች ያቀዳቸውን እቅዶች መነሻ በማድረግ የራሳቸውን ዕቅድ በመንደፍ ከኮሚቴው ጋር በቅንጅት በመስራት ህዝቡ የሚጠብቀውን ውጤት ለማምጣት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል አቶ ዳዊት አስፋው «ሁላችንም ተስፋ ሳንቆርጥ መሄድ እስካለብን ርቀት በመጓዝ፣ የምናገኘውን መረጃ በመለዋወጥ ለውጤታማነት መስራት አለብን» ብለዋል፡፡
የኮሚቴው ዋና ጸሐፊ አቶ ታምራት በቀለ እንደገለጹት፤ ተወዳዳሪ አትሌቶች ሲመረጡ ግልጽነትና ፍትሀዊነት ባለው መልኩ መሆን አለበት። የጨዋታው አዘጋጅ የሚያወጣውን የጊዜ ሰሌዳ የምዝገባና የመሳሰሉት ጉዳዮች ፣ ለውድድሩ የሚወጡ መስፈርቶችን በተለይም ከእድሜ ጉዳይ ጋር ያለውን ተጠንቅቆ በኃላፊነት በመስራት ህዝቡ የሚጠብቀውን ውጤት ለማምጣት ጠንክሮ በጋራ መስራት እንዳለባቸው አሳውቀዋል።
ፕሬዚዳንቱ ዶክተር አሸብር፤ የኮሚቴው አቅም በፈቀደ መጠን ለብሔራዊ ፌዴሬሽኖቹ የተቻለውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገቡ ሲሆን፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖቹም ከፊታቸው ላለው ውድድር በርትተው በመስራት ለለውጥ መትጋት እንዳለባቸው አሳስበዋል። የሚያገኙትን ገንዘብም በአግባቡ ሥራ ላይ በማዋል ለውጤት መትጋት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። ብሄራዊ ፌዴሬሽኖች ለጨዋታዎቹ እያደረጉ ያለውን ዝግጅት በቅርበት ለመከታተል ያመች ዘንድ በየጊዜው ለብሄራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ሪፖርት እንዲያደርጉም አሳስበዋል፡፡

ቦጋለ አበበ

Published in ስፖርት

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ዳኞችና ታዛቢዎች ሙያ ማህበር ከዛሬ ጀምሮ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚዘጋጅ ማንኛውንም ውድድር ለሦስት ሳምንት እንደማይመራ አስታወቀ። ትናንትን በተካሄደው ጉባዔ ዳኞች ዋስትና የማይሰጣቸው ከሆነና በክልል የፀጥታ ኃይሎች ከለላ የማይደረግላቸው ከሆነ በዳኝነቱ ላይ አይሳተፉም። ማህበሩ የአቋም መግለጫውን ያሳወቀው ትናንት በወቅታዊ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሮች ሳቢያ በዳኞች ላይ በሚደርሰው ጥቃት ምክንያት በጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ነው። 

ከጠቅላላ ጉባዔው አስቀድሞ የማህበሩን አባላት ያሳተፈ የውይይት መድረክ የተካሄደ ሲሆን፤ ከተሳታፊ ዳኞች መካከል በጨዋታዎች ጥቃት የደረሰባቸውም ተገኝተው ተሞክሯቸውን ገልጸዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለው የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ቀስ በቀስ እያደገ ዳኞችን እስከመደብደብ መድረሱ ተጠቁሟል። በተለይ በ19ኛ እና 22ኛ ሳምንት የፕሪምየር ሊጉ መርሐ ግብር በአዲስ አበባና ወልዲያ ስታዲየሞች ላይ የተከሰተው ችግር በመገናኛ ብዙሃን ስለተላለፈ እንጂ፤ በየክልሉ በርካታ በደሎች እንደሚደርስ ዳኞች ገልጸዋል። ይህ በአካል ላይ ጉዳት የሚያደርስና ለህይወትም የሚያሰጋ ጉዳይ በቀጣይ ዳኞችን ከማሳሰብ አልፎ ያለከለላና ዋስትና የማጫወት ስጋት ሊደቅንባቸው ችሏል።
በመድረኩ ላይ በተለይ ለችግሩ ምክንያት ናቸው ያሏቸውን ጠቁመዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ጥፋት የሚያጠፉ ተጫዋቾችና ክለቦች በፌዴሬሽኑ የሚጣልባቸው ቅጣት አነስተኛ ከመሆኑም በላይ በይግባኝ ሰሚ በኩል ቅጣቱ የሚሻርና የሚቀልላቸው መሆኑ በዋናነት ተጠቅሷል። በወቅቱ ሁኔታ ስፖርቱን ከፖለቲካ ለመለየት እንዳልተቻለና በክልል በሚካሄዱ ጨዋታዎች ላይ የሚገኙ የፀጥታ አካላት ከወገንተኝነት የጸዱ ባለመሆናቸው ውሳኔዎችን ለማስተላለፍ አስቸጋሪ እንዳደረገባቸውና የፀጥታ አካላትን አምኖ ጨዋታዎችን ማካሄድ የማይታሰብ እየሆነ መምጣቱንም ጠቁመዋል። የቡድን መሪዎችና አሰልጣኞች በቡድናቸው ላይ ያላከናወኑትን ሥራ በዳኞች ለማሳበብ መሞከራቸውም ሌላኛው ችግር ነው፡፡ ደጋፊዎችን ጭምር ለረብሻ የሚያነሳሱ ሆነዋል። በተለይ በክልሎች ያሉና አጥር የሌላቸው ሜዳዎች ተመልካች በቀጥታ ወደ ሜዳ ለመግባት ስለሚያመቸው ጥቃቱን ለመፈጸም ምቹ ሆነዋል።
የዳኞች ማህበሩ ችግሩ ጎልቶ እስኪታይ ድረስ ያከናወነው ነገር አለመኖሩም በድክመት መልክ ከተሳታፊዎቹ ተነስቷል። ማህበሩ ጠቅላላ ጉባዔውን ለመጥራት እጅግ ከመዘግየቱም ባለፈ ለአባላቱ ዋስትና ለማሰጠት ያደረገው ነገር አልነበረም። ሙያዊ ብቃትን በማሻሻል በኩልም እንዲሁ እጥረት እንዳለበት ነው የተጠቆመው። ዳኞች እርስ በርሳቸው የማይደጋገፉ በመሆናቸው ምክንያትም አንዱ ዳኛ ጥቃት እየደረሰበትም የሌሎች አለመተባበርም ተነስቷል። ጉዳት የደረሰባቸው ዳኞች ህክምናቸውን በራሳቸው ወጪ እንዲሸፍኑ መደረጉም በተመሳሳይ በዳኞቹ ዘንድ ቅሬታ ያስነሳ ጉዳይ ነበር።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲ ባሻ «ዳኝነት የተከበረ ሙያ ነው፤ እግር ኳስም ተወዳጅ ስፖርት ነው። የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር በፊትም የሚታይ ቢሆንም አሁን ግን መጠኑ በመጨመሩ አሳሳቢ ሆኗል። ፌዴሬሽኑም ይህንን የሚያወግዝ ሲሆን፤ ለአንድ ሳምንት ጨዋታውን ያቋረጠበት ምክንያትም ይኸው ነው» ብለዋል፡፡ ከመድረክ ለተነሱ ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል።
ረብሻው እንደ አገር እንጂ በእግር ኳስ ስፖርት ላይ ብቻ የታየ አለመሆኑና ስፖርቱንም ከፖለቲካ ማያያዝ እንደማይገባ ጠቁመዋል። የተጎዱ ዳኞች ህክምናም በፌዴሬሽኑ የሚሸፈን ይሆናል። ፌዴሬሽኑ በቀጣይ ከጸጥታ ኃይሎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። ፌዴሬሽኑ ዛሬ ከክለቦች ጋር ውይይት የሚያደርጉ በመሆኑም ማህበሩ ለውሳኔ እንዳይቸኩልም ነው የተናገሩት።
ወልዲያ ላይ ጥቃት የደረሰበት ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ለሚ ንጉሴ «ዳኝነት የህይወት መስዋዕትነት ሊከፈልበት የሚገባ ሙያ አይደለም። እኛ የፊፋን ህግ የሚተገብር ሙያተኞች እንጂ ጦር ሜዳ የዘመትን ወታደሮች አይደለንም» ሲል ሃሳቡን ገልጿል፡፡ አዲስ አበባ ላይ የተደበደበው ኢንተርናሽናል አልቢትር እያሱ ፈንቴ በበኩሉ «ስፖርቱን ከፖለቲካ መለየት አልቻልንም፤ ሁኔታው ሲፈጠር ቆሞ ከመመልከት ውጪ ሊገላግል የመጣም የለም የመከላከያው ፍፁም ገብረማርያም ብቻ ነው እገዛ ለማድረግ ሲጥር የነበረው» ብሏል፡፡
ከውይይቱ በኋላ በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይም ማህበሩ የደረሰበትን የአቋም መግለጫ አስታውቋል። በብሄራዊ ፌዴሬሽኑ የሚዘጋጁ ማንኛውንም ዓይነት ውድድሮች ላይ ለሶስት ሳምንታት (እስከ ግንቦት 20) በዳኝነት ላለመሳተፍ፣ ፌዴሬሽኑ የህክምና ጨምሮ ኢንሹራንስ እንዲኖራቸው፣ በ2010ዓ.ም የውድድር ዘመን የተጎዱ ዳኞች ተገቢው ካሳ እንዲሰጣቸው፣ ከክልል ፀጥታ ኃይል ጋር በመግባባት ዳኞች በሚሄዱበት አካባቢ ጥበቃ እንዲያደርግ፣ በወንዶች እና በሴቶች ፕሪምየር ሊግ ለመዳኘት በሚደረግ ጉዞ አውሮፕላን በሚደርስበት ቦታ ሁሉ እንዲመቻች፣ የፌዴራል ዳኛ እያሱ ፈንቴን ጉዳይ ጨምሮ ፖሊስ ያወቃቸው የስርዓት አልበኝነት የመብት ጥሰቶች ተገቢውን የህግ ፍርድ እንዲያገኙ፣ ፌዴሬሽኑ ለዳኞች እና ለታዛቢዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና እንዲመቻች፣ የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴዎቹ አሰራር በግልፅ እንዲታወቅ እንዲሁም ተገቢው የህግ ከለላ በሌለባቸው ስታዲየሞች ውድድር እንዳይካሄድ የሚሉ የአቋም መግለጫዎችም በማህበሩ ተይዘዋል። 

ብርሃን ፈይሳ

 

 

Published in ስፖርት
Thursday, 03 May 2018 16:52

የመስክ ጉዞና ጓዝ

‹‹መስክ ምንድነው?›› ከሚል ጥያቄ እንጀምር እንዴ? ኧረ ጎበዝ ይሄ እንግሊዝኛ እኮ ብዙ የአማርኛ ቃላትን አስረሳን፡፡ መስክ የሚለው ቃል ‹‹ፊልድ›› በሚል ቃል ተተክቷል፡፡ እኔ ደግሞ ‹‹ፊልድ›› እያልኩ አልጠቀም! በቃ መስክ በሚለው እንግባባና ወደ ጉዳያችን እንሻገር፡፡ 

ቆይ ግን የመስክ ጉዞ ያልሄደ አለ? ችግሩ እኮ የሄደውም ‹‹የጉዞ ማስታወሻ›› ብሎ ‹‹ጠመዝማዛውን የምንትስ መንገድ›› ከማለት በስተቀር መስክ በራሱ ጠመዝማዛ መሆኑን የሚናገር የለም፡፡
በየትኛውም ተቋም ውስጥ የመስክ ሥራዎች ይኖራሉ፡፡ እናም ብዙ ሰው ያውቀዋል ብዬ ነው፡፡ በመስክ ጉዞ ውስጥ የምታዘባቸው ብዙ ነገሮች አሉ (መታዘብ ስወድ)፡፡ ከጉዞው ቀን ጀምሮ እስከ ዋናው ክንውን ድረስ ያለ ጣጣ፡፡ ከምንም በላይ ግን የሚያናድደኝ ጉዞ ላይ ያለው ጣጣ ነው፡፡ ከዚህ ይጀምራል፡፡
የጉዞው መነሻ ቦታና ሰዓት ይነገራል፡፡ ብዙ ጊዜ ልብ ብላችሁ ከሆነ የመነሻ ሰዓት የሚባለው ደግሞ 12፡00 ነው (እስከ 3፡00 እኮ ሊዘገይ ይችላል)፡፡ በነገራችን ላይ እኔ ቀድሜ በመድረስ ብዙ ጊዜ ክስረት ደርሶብኛል (የጊዜ ክስረት ማለት ነው)፡፡ በእውነት ሰዓት አክባሪ በመሆኔ ተበድያለሁ (ጅል ሆንኩ ማለት ነው ብዬም አስቤ አውቃለሁ)፡፡ ታዲያ ምን ይደረግ ሰዓት አለማክበር እኮ እንደ አራድነት ተቆጠረ፡፡ ቀድሞ የደረሰ ሰው እንግዲህ መኪና ውስጥ ይገባል፣ ይወጣል፣ ይንቆራጠጣል፣ ሰዓቱን ያያል፤ ምን ዋጋ አለው አብዛኛው ተጓዥ አልመጣ፡፡
አስተባባሪ ይደውላል፡፡ ‹‹እየመጣን ነው›› ይባላል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ጭራሽ የሚቆጣም አይጠፋም፡፡ እኔ ብሆን ግን ይህን ሰው ትቼው ነበር የምሄደው፡፡ ከመጣ በኋላ እንኳን እንደገና የሚጠፋው ሰዓት ቀላል አይደለም፡፡ አንዱ አንዱን ሊጣራ ይሄዳል፤ በዚያው ይጠፋል፣ አሁንም እሱን ፍለጋ የሄደው ሰው በዚያው ይጠፋል፡፡ ከብዙ መደዋወልና መጠራራት በኋላ ሁሉም ይሰባሰባል፤ እንዲህ እንዲህ እያለ እንደምንም ጉዞው ይጀመራል፡፡
ጉዞው ተጀመረ ማለት ጓዙ አለቀ ማለት እንዳይመስላችሁ (ዋናው ጓዝ ነው የተጀመረው)፡፡ መኪናው ገና ትንሽ እንደሄደ ጣጣው ይጀምራል (ይሄ ትዝብት የአውሮፕላን ጉዞን አይጨምርም ማለት ነው)፡፡ ኧረ ስንት ዓይነት ባህሪ አለ ጎበዝ! ደግሞ እኮ ያ አርፍዶ ሰውን ሲያጉላላ የነበረው ሰው ነው ከመጣ በኋላም ጣጣው የሚበዛ፡፡ ገና ትንሽ እንደሄደ ‹‹ቁርስ የት ነው የምንበላው›› ማለት ይጀምራል (ያን ያህል ሲያረፍድ አይበላም ነበር እንዴ?) እሺ የቁርስ ነገር የጋራ ጉዳይ ነውና ችግር የለውም፡፡ አንዳንዱ ግን በዚህ አጋጣሚ የግል ጉዳዩን ለማስፈጸም አቁሙልኝ የሚልም አለ፡፡
ያው መቼም የቁርስ ነገር የግድ ነውና መኪናው ለቁርስ ይቆማል፡፡ እዚህ ላይ አንድ የተለመደ (ግን የማይተገበር ነገር) አለ፤ ‹‹ለቁርስ ይህን ያህል ደቂቃ›› ይባላል፡፡ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ‹‹ስንት ዓይነት ሰው አለ›› ማለት፡፡ አንዳንዱ እኮ ከማናደድ አልፎም ያስቃል፡፡ መጀመሪያ ‹‹እኔ ቁርስ አልበላም›› ይላል፡፡ ‹‹ኧረ ግድየለህም ወደ በረሃ ነው የምንገባው ብላ›› ሲባል ‹‹ካራ በአንገቴ›› ብሎ ድርቅ፡፡ እንግዲህ እምቢ ካለ ምን ይደረጋል ተብሎ ሌላው ይበላል፡፡ ሁሉም ጨርሶ ሊገባ ሲል ያ ሰው ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው? ባለቀ ሰዓት ቁርስ ሊበላ ያዛል፡፡ ቶሎ የሚደርስ ነገር ቢያዝስ ጥሩ አልነበር፤ በቃ በጣም የሚያቆይ ነገር ያዛል፡፡
መቼም ይህን ሰው መጠበቃችን አልቀረ በማለት የጨረሱት ሰዎች ደግሞ እንደገና ሌላ ነገር ይጀምራሉ፤ ግማሹ ሱቅ ይሄዳል፤ አንዳንዱም ማኪያቶ፣ ቡና፣ ሻይ እያለ ይበታተናል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ለቁርስ ከተባለው ሰዓት ሦስት አራት እጥፍ ይራዘማል፡፡ በአንድ ሰው ምክንያት ብዙ ሰው ይጉላላል፡፡ ይህን ሁሉ ሲያደርግ ሰው እየጠበቀኝ ነው እንኳን አይልም፡፡ ይሄንንማ ትቶ ነበር መሄድ ያሰኛል፡፡
በብዙ ጭቅጭቅ እንደምንም የቁርስ ሰዓት የተባለው ምሳ ሰዓት ይደርስና ጉዞ ይጀመራል፡፡ ትንሽ እንደሄደ ደግሞ የምሳ ሰዓት ተብሎ ይቆማል፡፡ እንዲያውም የምሳ ሰዓት ላይ ደግሞ የባሰ ጊዜ ነው የሚባክነው፡፡
ቆይ ግን በእንዲህ አይነት ጉዞ ላይ የሄድንበትን ጉዳይ ለምን የሌላ ሰው ሥራ አድርገን እናየዋለን? ለምሳሌ የምንሄድበት አካባቢ በረሃማ ሊሆን ይችላል፤ የምንሄድበት ቦታ ብዙዎቻችን የማናውቀው ሊሆን ይችላል፡፡ በረሃማውን አካባቢ ፀሐይ ሳይጠነክር ማለፍ የሚጠቅመው ማንን ነው? ተጓዡን እኮ ነው፡፡ የማናውቀው ከተማ ውስጥ ያለሰዓት ብንገባ መጉላላት የሚደርሰው እኮ ተጓዡ ላይ ነው፡፡
ይሄ እንግዲህ ገና ስንሄድ ያለው ጣጣ ነው፡፡ በዋናው ዝግጅት ላይ የሚኖረውን ውጥንቅጥ እንለፈውና ዝግጅቱ አልቆ መመለስ ላይ ያለውን ጉዞ ደግሞ ልብ እንበል፡፡ ይሄኛው ጉዞ ደግሞ ሲሄዱ ከሚኖረው ይበልጣል፡፡ በመጀመሪያ ተጓዦችን ማሰባሰብ በራሱ አሰልቺ ነው፡፡ የመመለሻ ቀን ሁሉም ከአንድ ቦታ ስለሚገኝ ይመስላል ብዙ ጊዜ 11፡00 ወይም 10፡00 ይባላል፡፡ በቃ የመመለሻ ቀን ዕለት እንቅልፍ የሚባል ነገር የለም፡፡
አስተባባሪው 10፡00 መጥቶ ያንኳኳብሃል፤ አንተ ትነሳለህ፡፡ አንተ ሌሊት የተነሳህ እንግዲህ ጠዋት 1፡00 የሚነሳውን ሰው ቁጭ ብለህ መጠበቅ ነው፡፡ ሌሊት ላይ ‹‹እየተነሳሁ ነው›› ማለት የጀመረ ረፋድ ይሆናል፡፡ ለነገሩ ልተኛ ብትል እንኳን መተኛት አትችልም፤ የበር መንኳኳት ይረብሻል፡፡ ይህን ሁሉ ተቋቁመው ግን የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ በማለት ዝም የሚሉም አሉ፡፡
እንዳልኳችሁ ሲመለሱ ያለ ጉዞ ጣጣው ይበዛል፡፡ በዚህኛው ጉዞ ደግሞ አሰልቺው ነገር ሱቅ እና የገበያ ቦታ በተገኘ ቁጥር የሚቆመው ነው፡፡ የተሄደበት ዋና ዓላማ ንግድ እስከሚመስል ድረስ ትኩረቱ ሁሉ የገበያ ዋጋ ላይ ይሆናል፡፡ ከዚያ ውስጥ የቸኮለና ሥራ ያለው ሰው እንሂድ ብሎ ቢለፈልፍ ማንም አይሰማውም፡፡
እንግዲህ ካነሳነው አይቀር እዚህ ላይማ ብዙ ነገር ይወራ፡፡ በመስክ ሥራ ሰበብ ከቢሮ ሥራ ለመገላገል የሚፈልገው ቀላል አይደለም፡፡ እንዲያውም ቶሎ ከመድረስ ይልቅ እንደገና ደግሞ ሌላ ከተማ ውስጥ ማደር የሚፈልጉ አሉ፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን ቢሮ ውስጥ ያለው ሥራ ተዳፍኖ ነው፡፡ የመስክ ሥራው ከታሰበለት ቀን በላይ ሊሆን ይችላል ማለት ነው፡፡ በስንት ጸሎት ያገኘውን ሥራ ለመሸሽ እንዲህ አይነት ማሰበቢያ ይፈልጋል፡፡ ይሄ ማለት ሁሉም ላይሆን ይችላል፡፡
የተወሰነ ሰው ቶሎ መድረስ ቢፈልግ አይችልም፡፡ ምክንያቱም የሚያጓትተው ሰው ይበዛል፡፡ በተለይ የገበያ ነገር ይገርመኛል፡፡ አንዳንዱ የማይገዛውን ሁሉ እየዞረ ይጠይቃል፡፡ በተለይ ሴቶችማ በጣም ያበዙታል፡፡ አንድ ነገር ለመግዛት ዘጠኝ ሱቅ ነው የሚዞሩት፡፡ ደግሞስ አንድ ጊዜ ገዝተው ቢጨርሱ፤ አሁንም ሌላ ሱቅ ካገኙ መኪናው እንድቆም ያዝዛሉ፡፡ እኔማ በቃ የገበያ አካባቢ በደረስን ቁጥር እንዴት እንደምናደድ! ገና ከርቀት ሱቅ ነገር ካየሁ እንዳያዩት በወሬ እይዛቸዋለሁ፡፡
ጉዞውን የሚያጓትተው ገበያ ብቻ እንዳይመስላ ችሁ፤ በቃ እዚህ ግባ የማይባል ነገር ሁሉ ነው፡፡ ኧረ ይግረማችሁ ዛፍ ባገኙ ቁጥር ‹‹ቆይ አንዴ ፎቶ ልነሳበት!›› የሚሉ ሁሉ አጋጥሞኛል፡፡ እስኪ አስቡት ጸሐይ እየወጣና ብዙ ጉዞ ወደፊት እያለ በየዛፉ ሥር እሷን ፎቶ ማስነሳት ደግ ነው ትላላችሁ?

ዋለልኝ አየለ

 

Published in መዝናኛ

በኢትዮጵያ ህዝብ ማህበራዊ ትስስር ውስጥ ጎልተው ከሚታዩ የመረዳዳትና የህብረት መገለጫዎች አንደኛው ዕድር ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ በአዲስ አበባ በ117 ወረዳዎች ሰባት ሺ 500 የተመዘገቡ እድሮች አሉ፡፡ በከተማዋ ዕድር ምክር ቤት የተመዘገቡት እነዚህ ይሁኑ እንጂ ወደ ሁለት ሺ ያህል ያልተመዘገቡ ዕድሮች በየአካባቢው መኖራቸው ይጠቀሳል፡፡
ዕድር በመኖሪያ ወይም በስራ ቦታ በሚኖር ቅርበትና የዕለት ተዕለት ግንኙነት አማካኝነት ይመሰረታል፡፡ ዕድሮች ዋና አላማቸው ከሞትና ከቀብር ማስፈጸም ጋር የሚያያዙ ጉዳዮች ላይ መተጋገዝ ላይ ብቻ ተወስኖ ቆይቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ዕድሮች በበጎ አድራጎት፣ ማህበራዊ ችግሮችን በሚፈቱ ስራዎች ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስተባባሪነት በከተማዋ የዕድሮች ሲካሄድ የቆየው ‹የሰላምና የልማት ንቅናቄ› በተጠናቀቀበት ወቅት ዕድሮች ከነበራቸው ከሞት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ውጪ ተጨማሪ የማህበረሰብ ተሳትፎ ስራዎች ላይ የተሳተፉ ዕድሮችን በመምረጥ ተሸልመዋል፡፡ በአንደኝነት የተሸለመው የአቃቂ ቃሊቲ የስላሴ ዕድር ሲሆን ለግንባር ቀደም እጩነት ያበቃውም ለወጣቶች የስራ እድል በመፍጠሩ፥ የትምህርት ዕድል በማመቻቸቱና በበጎ ፈቃደኝነት በሚያደርጋቸው ሰናይ ተግባራቱ ነው፡፡
ከተመሰረተ የስድስት ዓመታት እድሜ ብቻ ያለው ይኸው መረዳጃ እድር ከሰራቸው አኩሪ ተግባራት መካከል በተለይም ከአረብ አገር ተመላሽ ለሆኑ 30 ወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር ራሳቸውን አገራቸውን እንዲረዱ ማድረጉ ነው፡፡ እድሩ 26 ሴቶችና አራት ወንዶችን በማደራጀት ስራ እድል እንዲያገኙ አመቻችቷል፡፡ ለወጣቶቹ የዘይት መጭመቂያ ማሽን በሁለት መቶ 50 ሺ ብር በመግዛት እንዲሰሩበት አበርክቶላቸዋል፡፡
ወጣት ሄኖክ ሙሉጌታ የስላሴ ዕድር ውስጥ በበጎ ፈቃደኝነት በሚሰሩ ስራዎች ላይ ከሚሳተፉ ወጣቶች አንዱ ነው፡፡ ዕድሩ ወጣቶችን በሰፊው እንደዲሳተፉ እንደሚያደርግ ይናገራል፡፡ ሄኖክና ሌሎች ወጣቶችም በእድሩ አሰባሳቢነት በበጎ ፈቃድ በአካባቢው ለሚገኙ ህሙማንና አረጋውያንን ይረዳሉ፡፡ በህመም ምክንያት ቤት የቀሩ ሰዎችን የመንከባከብ፣ መድሃኒቶችን አፈላልጎ በመግዛት ያግዛሉ፡፡ የመታከም አቅም ለሌላቸው ደግሞ የህክምና ወጪዎችን ለመሸፈን ሃብት የማፈላለግ ስራም ይሰራሉ፡፡
መረዳጃ እድሩ የአካባቢው ወጣቶች ራሳቸውን የሚለውጡበትን እድል ማመቻቸት ላይ ትኩረት እንዳደረገ የሚገልፀው ወጣቱ፤ ወጣቶች የስራ ባህልን እንዲያዳብሩም የተለያየ ስራ ይሰራል፡፡ ለአብነትም የአካባቢው ወጣቶች መቀሌ፣ ባርዳር፣ ሐዋሳ፣ ይርጋለምና ሌሎች አካባቢዎች ከሚገኙ ወጣች ጋር የልምድ ልውውጥ ማድረጋቸውን ነው የሚጠቅሱት፡፡
ወጣት ሄኖክ እንደሚናገረው፤ ዕድሩ ከተቋቋመ አጭር ጊዜና የዕድሩ አባላት መዋጮ አነስተኛ ቢሆንም የሚሰራው ስራ በርካታ ሲሆን ለውጥም ማምጣት ችሏል፡፡ እድሩ ትኩረቱን ያደረገው ከሞት በፊት ባሉ ስራዎች፣ መረዳዳትና የወጣቶችን የተጠቃሚነት ማስፋት ላይ ይሰራል፡፡ ወጣቶች እንዲማሩ፣ ወደ ስራ ሲገቡ እንዳይቸገሩ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግም ያግዛል፡፡ ለአካባቢው ወጣቶች ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑና አካባቢያቸውን በመጠበቅ ህብረተሰቡን የሚጠቅም ስራ እንዲሰሩ በማድረጉና ባመቻቸው እድል በርካታ ወጣቶች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
በዕድር አቅም ይህንን ማድረግ ከተቻለም በሌሎች መሰረታዊ የማህበረሰቡን ችግሮች በሚፈቱ ተግባራት ላይ ዕድሮች የጎላ ተሳትፎ እንዲኖራቸውም ሊታገዙ እንደሚገባ ወጣት ሄኖክ ይናገራል፡፡ በተለይ የወጣቶች የስራ ፍላጎት፣ የፈጠራ ሃሳባቸው እንዲሳካና ውጤታማ እንዲሆኑ ከዕድር አንስቶ በየደረጃው እገዛ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ያመለክታል፡፡
የስራ እድሉ ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል ሀይማኖት ደምሴ አንዷ ናት፡፡ ወጣቷ እንደምትናገረው፤ ከዱባይ ቤሩት ለስድስት አመታት ተዘዋውራ ብትሰራም ከእንግልትና ከመንከራተት ውጭ ይሄነው የሚባል ትርፍ አላገኘችም፡፡
ከአረብ አገር ከተመለሰች በኋላ ስራ በማጣቷ ምክንያት ተመልሳ መሄድ ታስብ እንደነበር የምትናገረው ወጣት ሃይማኖት፤ እርሷና ሌሎች የአካበቢው ወጣቶች ስራ በማጣት ተስፋ በቆረጡበት ወቅት እንዲህ አይነት የስራ እድል ያመቻቻል ብለው እንዳልጠበቁ ትገልፃለች፡፡ ከዕድር የተለመደ አሰራር ውጭ የስራ እድሉ ተጠቃሚ በመሆኗም የእድለኝነት ስሜት እንደተሰማት አመልክታ ‹‹እድሩ ይሄንን ያህል ካገዘ መንግስትም ሊደግፈን ይገባል›› በማለት ታስገነዝባለች፡፡
ወጣት ሀይማኖት እንደምትናገረው፤ የዘይት መጭመቅ ስራ ከመግባታቸው በፊት ስልጠና ወስደዋል፡፡ በቅርቡም የመስሪያ ቦታ የተሰጣቸው ሲሆን በአሁኑ ወቅት የመስሪያ ቦታው ከዚህ ቀደም ሌላ ስራ ሲሰራበት የነበረ በመሆኑ ለዘይት መጭመቂያ እንዲሆን ለማስተካከል ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ የብድር አገልግሎት ለማግኘትም ጥረት ቢያደርጉም እስካሁን አልተሳካላቸውም፡፡ የኤሌክትሪክ አቅርቦትም እንዲቀርብላቸው እገዛ ይፈልጋሉ፡፡
የስላሴ ልማታዊ እድር ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌታቸው መኮንን በበኩላቸው፤ የእድሉ አባላላት በእድሜ ከፍ ያሉ ቢሆኑም እድሩ በሚሰራው ስራ ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆኑት በይበልጥ ወጣቶች መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ዕድሩ ለ2ሺ500 የአካባቢው ወጣቶች የትምህርት እድል እንዲያገኙ ማድረጉንም ያስረዳሉ፡፡
ትምህርታቸውን ያቋረጡና ውጤት ያመጡ ወጣቶች በእንጨት ስራ፣ በብረታብረት፣ በምግብ ዝግጅትና በሌሎችም የትምህርት ዘርፎች በግል የትምህርት ተቋማት የሙያ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ መደረጉንም ይጠቅሳሉ፡፡ «ወጣቶቹ የትምህርት ወጪያቸውንና ወደ ስራ ሲገቡ የስራ ማስጀመሪያ ገንዘብ በዕድሩ የተሸፈነ ነው» የሚሉት አቶ ጌታቸው፤ ይህም የተገኘው እድሩ ከተለያዩ ተቋማት ጋር የኃብት ማፈላለግ ስራ በመስራት መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡ በዚህም ወጣቶች ራሳቸውን ችለው ቤተሰባቸውን እንዲያግዙና ለተሻለ ውጤት እንዲነሳሱ መደረጉን ያመለክታሉ፡፡
ዕድሩ ከሞት ባለፈ በወጣቶች ላይ እንዲሰራ ያደረገው በአካባቢው ያለው ችግር መሆኑን የሚገልጹት አቶ ጌታቸው፤ ወጣቶች ትምህርታቸው በማቋረጥ እቤት እንዳይውሉና አካባቢው ያለውን ነገር በመጠቀም ወደ ስራ እንዲቀይሩት በማሰብ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ «ወጣቶች ከሱስ ተጠብቀው በአካባቢው ያሉ ችግሮችን ወደ ስራ እንዲቀይሩ ያግዛል፡፡ ዕድሩ የስራ እድል ፈጠራውን ከወጣቶች ስብዕና ግንባታ አንጻርም እያከናወነ ይገኛል» ይላሉ፡፡ በአካባቢው ለተለያዩ ሱሶች የተጋለጡ 16 ወጣቶችንም በማሰባሰብ በመኪና ጥበቃ አገልግሎት እንዲሰሩ መደረጉን ጠቅሰው፤ ወጣቹ በማህበር ተደራጅተው በመስራት ከሁለት መቶ ሺ ብር በላይ ካፒታል አላቸው፡፡
እንደ አቶ ጌታቸው እምነት፤ በከተማዋ በርካታ ዕድሮች ቢኖሩም ወጣቶች መስራት የሚቻለውን ያህል እየተሰራበት አይደለም፡፡ በተለይም ዕድሮች ከያዟቸው የህብረተሰብ ክፍል ብዛት አንጻርም ያሉትን የወጣቶች ችግሮች ለመፍታት ብዙ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ እድሮች ከሞት ጋር ከተያያዙ ስራዎች ወጥተው ወጣቶችን፣ አካባቢንና አገርን የሚጠቅም ስራ እንዲሰሩ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡
በወጣች የስራ ፈጠራ ላይ የሚሰሩ ስራዎችን በትክክል ውጤታማ ለማድረግ እንዲህ አይነት የተጀመሩ ስራዎችን መደገፍ አስፈላጊ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ወጣቶችን በማሰባሰብ የሚሰሩት ስራ ውጤታማ እንዲሆን የግድ የመንግስት ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ያስረዳሉ፡፡ የተጀመሩ የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ስራዎችን ታች ድረስ በማውረድ በየአካባቢው የሚገኙ ዕድሮችን በመደገፍ ማስፋፋት እንደሚቻልም ይጠቁማሉ፡፡
የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከአዲስ አበባ ዕድሮች ምክር ቤት ጋር በጋራ ባዘጋጁት የዕድሮች የሰላምና የንቅናቄ ዝግጅት ላይ የተሳተፉ አካላት በበኩላቸው፤ ዕድሮች በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ፈቺነትና የስራ እድል ፈጠራ ላይ የጎላ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እገዛ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡ ከተለመደው የቀብር ማስፈጸም ተግባር ባለፈ የልማት ተሳታፊ እንዲሆኑ ማሳተፍ እንደሚገባም፣ ዕድሮች ማህበራዊ ችግሮችን በሚቀርፉ ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ የሚያደርግ አሰራር ምቹ እዲሆን እና ዕድሮች ከአካባቢያዊ ችግሮች በመነሳት በበጎ አድራጎትና በስራ ፈጠራ ስራዎች ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ በህግ ማዕቀፍ መደገፍ እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡
በተጨማሪም ዕድሮች ያላቸውን የሰው ኋይልና የተከማቸ ገንዘብ ውጤት እንዲያመጣ ሊጠቀሙ የሚችሉበት እድል ሊመቻች እንደሚገባና የህብረተሰቡን ችግር በህብረተሰብ ተሳትፎ ለመፍታት ዕድሮችን እንደዋነኛ መንገድ መጠቀም እንደሚስፈልግ ተገልጿል፡፡

ሰላማዊት ንጉሴ

Published in ማህበራዊ

በከተሞች እያደገ የመጣውን የቤት እጥረትና ተጓዳኝ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል የተቀናጀ የቤቶች ልማት ፕሮግራም በአገር አቀፍ ደረጃ ተነድፎ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ከዛሬ አሥራ ሦስት ዓመት በፊት ይፋ ሲደረግ በፕሮግራሙ ተጠቃሚ ለመሆን ከ453 ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎች የተመዘገቡ ቢሆንም፤ አሁንም ድረስ የዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን የቻሉት 20 በመቶ እንኳን አይደርሱም፡፡

ይህ እቅድ በበቂ ሁኔታ ተግባራዊ መሆን ባልቻለበት ሂደት የቤት ግንባታው ቁጠባን መሰረት ባደረገና አማራጭ የቤት ግንባታዎችን ለህዝቡ እንደየአቅሙ ለማቅረብ እንዲሁም የመጀመሪያው ዙር ተመዝጋቢዎች የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት በሚል በ2005 ዓ.ም ድጋሚ ምዝገባ ተካሂዷል፡፡ በዚህም ወቅት በ1997 ዓ.ም ቤት ተመዝጋቢዎች በተጨማሪ አዲስ ተመዝጋቢዎች ከ10/90 እስከ 40/60 ብሎም በማህበራትም በመደራጀት የቤት ባለቤት ለመሆን እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡
ሆኖም ግን ግንባታውን እንዲያካሂድ ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም ለህዝቡ ቃል የገባውን ተስፋ ጠብቆ መጓዝ ስለተሳነው ቁጥር ዜጎች ያስተዳድረናል በሚሉት መንግሥት ላይ እምነት እንዲያጡ ምክንያት ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል በቤቶቹ ግንባታ መጓተት ተስፋ የቆረጡ በርካታ ተመዝጋቢዎች ቁጠባቸውን በተፈለገው ደረጃ ካለመቆጠባቸውም ባለፈ፤ የቆጠቡትንም ከባንክ እያወጡ ይገኛሉ፡፡
ለዚህ ደግሞ በዋነኝነት የመኖሪያ ቤት የግንባታ ሂደት በሙስና እና ብልሹ አሰራር የተተበተበ መሆኑ በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡ ሰሞኑን በፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ይፋ የተደረገው የጥናት ሪፖርት እንደሚያሳየውም የቤት ልማት ፕሮጀክቱ በሙስና እና በብልሹ አሰራር ምክንያት የታሰበውን ግብ እየመታ አይደለም፡፡ ጥናቱ 18 ቁልፍ ችግሮች የዘርፉን ልማት እየጎተቱት መሆኑን ያሳያል፡፡
በኮሚሽኑ የሙስና መከላከል ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ወንድይራድ ሰይፉ እንደሚናገሩት፤ ለሙስናና ብልሹ አሰራር እየዳረጉ ካሉ ክፍተቶች መካከል የተመዝጋቢዎች የመረጃ አያያዝ ችግር አንዱ ነው፡፡ በ1997 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጋራ መኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ለመሆን የቤት ፈላጊዎች በሚመዘገቡበት ወቅት የራሱ የሆነ መለያ ቁጥር በተመዘገቡበት ክፍለከተማ ስም በመስጠት (ቢጫ ካርድ) በተመዝጋቢዎች መረጃ ቋት ውስጥ እንዲሰፍር ተደርጓል፡፡
ሆኖም ቀደም ባለው የተቋሙ አሰራር ተመዝጋቢዎች ያላቸውን መረጃ የሚያውቁበት ሥርዓት ያልተዘረጋና በመረጃ ቋት የተያዘ መረጃ እንዳይለዋወጥ ወይም እንዳይነካካ የሚያደርግ የውስጥ ክትትልና ቁጥጥር ያልነበረ በመሆኑ፣ በአንድ ተመዝጋቢ ቁጥር ላይ የሌላ ግለሰብ ስም ተመዝግቦ የሚገኝበት ሁኔታ ተከስቷል፡፡ ለአብነት ያህልም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በምዝገባ ቁጥር 04/8183 የተመዘገቡት ግለሰብ ፤ በሌላ ግለሰብ ስም ተተክተው እንደሚገኙ ቀደም ሲል ኮሚሽኑ ባካሄደው ጥናት አረጋግጧል፡፡
ተቋሙ ይህንን ጥናት ካካሄደ በኋላ ከምዝገባ ጋር ተያይዞ ከህብረተሰቡ በተደጋጋሚ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመቅረፍና ቀደም ሲል የተካሄደን ምዝገባ ለማጥራት በማሰብ በ2005 ዓ.ም በድጋሚ እንዲመዘገቡ ከመደረጉም ባሻገር የተመዝጋቢዎች መረጃ ከተቋሙ አሰራር ጋር ገለልተኛ ከሆነው የመረጃ ደህንነት መረብ ኤጀንሲ ጋር እንዲያያዝ በማድረግ በማይመለከተው አካል መረጃው እንዳይነካካ ለመከላከል ጥረት ተደርጓል፡፡ ይሁንና አሰራሩን ለማስተካከል የተወሰደው እርምጃ ችግሩን ሙሉ ለሙሉ የፈታው ባለመሆኑ አሁንም አንዳንድ ግለሰቦች በ1997 ዓ.ም ተመዝግበው ስማቸው በምዝገባ ዝርዝር ውስጥ እንደሌለ ቅሬታቸውን በማቅረብ ላይ መሆናቸውን አቶ ወንድይራድ ያመለክታሉ፡፡ ይህም ህብረተሰቡ በመንግሥት አሰራር ላይ እምነት እንዳይኖረው የሚያደርግ ከመሆኑም በተጨማሪ ግልፅነትና ተጠያቂነት ለሌለው አሰራር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ይጠቅሳሉ፡፡
ሌላው በጥናቱ የተለየው ችግር ደግሞ የግል የመኖሪያ ቤት ያላቸውንም ሆነ የልማት ተነሺዎችን የመመዝገብና የማጣራት ሥራ ክፍተት ያለው መሆኑን ነው፡፡ በመንግሥት ከፍተኛ ድጎማ ተደርጎባቸው በሚገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተጠቃሚ ለመሆን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በራሱ ወይም በትዳር ጓደኛው ስም የመኖሪያ ቤት ወይም የቤት መስሪያ ቦታ የሌላቸው ግለሰቦች መሆን እንዳለባቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተቀናጀ የቤት ልማት ፕሮግራም መመሪያው እንደሚያዝ ያስረዳሉ፡፡
በተመሳሳይ የልማት ተነሺዎች የኮንዶሚኒየም ቤት ተጠቃሚ የሚሆኑት በክፍለከተማ መሬት ልማት ባንክና ከተማ ማደስ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አማካኝነት የቦታ ከለላ ተደርጎ የነዋሪዎች ዝርዝር ባሉበት የቤት ዓይነት ማለትም የግል ይዞታና የቀበሌ ቤት ተከራይ በሚል ምዝገባ ከተካሄደ በኋላ የቀበሌ ቤት ተከራዮች ህጋዊነት በወረዳ ቤት ማስተላለፍ አስተዳደር ንዑስ የሥራ ሂደት እንዲረጋገጥ በማድረግ እንደምርጫው የኮንዶሚኒየም ወይም የቀበሌ ቤት ወይም የካሳ ክፍያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡
ይህም አሰራር ለክፍለ ከተማ መሬት ልማት ባንክና ከተማ ማደስ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተደራራቢ ኃላፊነቶች በመስጠት ሂደቱ ለክትትልና ቁጥጥር የማይመች፣ በግል ባለይዞታዎች ላይ በሦስተኛ ወገን የማጣራት ሥራ ስለማይሰራ ያለአግባብ ግለሰቦች የቤት ወይም የካሳ ክፍያ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩን ይጠቅሳሉ፡፡ በተጨማሪም በኮንዶሚኒየም ቤቶች ላይ የዕጣ ማውጣት ሥራ የሚከናወነው ግንባታቸው 80 በመቶና ከዚያ በላይ በሆኑ ቤቶች ላይ በመሆኑና የቀበሌ ቤት ተከራይ የተባሉት ግለሰቦች ከዚህ በፊት የኮንዶሚኒየም ቤት ተጠቃሚ አለመሆናቸውን የማረጋገጥ ሥራ የተጠናከረ ሥርዓት አልተዘረጋም፡፡ በዚህም ምክንያት የቤቶች ግንባታ እስኪጠናቀቅ በመሀል በሚኖር የጊዜ ክፍተት የልማት ሥራ ተነሺ የሚሆኑ ግለሰቦች ሳይገባቸው ዳግም ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙ በምርመራ መረጋገጡን ነው የሚያመለክቱት፡፡
«ለምሳሌ በልደታ ክፍለከተማ ከቀበሌ 39/49 ከ 942 የልማት ተነሺዎች መካከል በኮሚሽኑ በተካሄደ ጥናት በናሙና ተመርጠው የማጣራት ሥራ ከተካሄደባቸው 150 ግለሰቦች መካከል ሦስት ግለሰቦች በገላንና ጆሞ ሳይቶች ላይ በአምስተኛ ዙር የዕጣ ዕድለኞች እንደሆኑ በምርመራው ተረጋግጧል» ይላሉ፡፡
እንደ አቶ ወንድይራድ ገለፃ፤ ማንኛውም ግንባታ ለመጀመር ዲዛይኑ በጥንቃቄ ካልተዘጋጀ በቀጣይ የግንባታ ሂደቶች ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችል እሙን ነው፡፡ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ዘርፍም አርክቴክቸራል፤ ስትራክቸራል፣ ሳኒተሪና ኤሌክትሪክ ዲዛይኖች እንዲሁም አጠቃላይ የየሳይቱ የፍሳሽ የውሃና የኤሌክትሪክ ዲዛይን ሥራዎች ይሰራሉ፡፡ እነዚህ መጠነ ሰፊ ሥራዎች በጥንቃቄ ስለመሰራታቸው በተቋሙ የሚደረግ የውስጥ ቁጥጥር ስርዓት የተጠናከረ ባለመሆኑ ላልተገባ የሥራ መጠንና ዋጋ ልዩነት ዳርጓል፡፡ ከዚህም ባሻገር በተደጋጋሚ የዲዛይን ክለሰ እና የግንባታ ማጠናቀቂያ ጊዜ እንዲራዘም ተደርጓል፡፡
ለአብነት ሲጠቅሱም «በጉለሌ ጽሕፈት ቤት ስር በመገንባት ላይ ካሉ ብሎኮች መካከል አንድ ብሎክ የኮለን ሺፍቲንግ ያጋጠመው በመሆኑ መዋቅሩ አስተማማኝ መሆን በሚችል መልኩ ዲዛይኑ እንዲከለስ እንዲሁም በኮዬ ፈጬ ሳይት ላይ በመገንባት ላይ ያሉ የአምስት የጣራ ዲዛይን ችግሮችን ለመፍታት ቀደም ብሎ የተሰራው ዲዛይን እንዲሻሻል ተደርጓል» ብለዋል፡፡
ሌላው ጥናቱ ያየው ክፍተት ደግሞ በቅድሚያ ባልፀደቀ ንድፍ ግንባታ መፈፀም ነው፡፡ አማካሪ መሀንዲሶች በግንባታ ሂደት የሚያጋጥማቸውን ችግር ለመቅረፍ ከግንባታው መጠን እስከ 10 በመቶ ድረስ የሥራ ለውጥ ትዕዛዝ በመስጠት ችግሮችን መቅረፍና ለአሰሪው አካል ሁኔታውን ማሳወቅ እንደሚገባቸው አቶ ወንድይራድ ይገልፃሉ፡፡
ሆኖም አልፎ አልፎ በአሰሪው ተቋም የሚደረግ ክትትል የተጠናከረ ባለመሆኑ አማካሪ መሐንዲሶች ለአሰሪው ተቋም ስለተደረገ የማሻሻያ ሥራ ወይም የሥራ ትዕዛዝ ለውጥ ሳያውቁ ግንባታውን በመቀጠል ሥራው ከተሰራ በኋላ አዘጋጆች በማምጣት ክፍያ እንዲፈፀም እንደሚጠይቁ ያስረዳሉ፡፡ ይህም በተቋሙ በተቀመጠ የጥራት ደረጃ መሰረት ሥራዎች ስለመሰራታቸው ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ሁኔታ የሚፈጥር ከመሆኑም በተጨማሪ ባልፀደቀ ዲዛይን ክፍያ ስለሚፈፀም በተቋራጩና በአሰሪ ተቋም መካከል በሚፈጠር አለመግባባት የማጠናቀቂያ ጊዜ የሚራዘምበት ወይም ላልተገባ ድርድር ምቹ ሁኔታን የሚፈጥርበት አጋጣሚ እንዲኖር አድርጓል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሥራ ላይ የሚሳተፉ የተቋራጮች ምልመላ በፕሮጀክቱ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ተቋራጮች በፕሮጀክቱ ጽሕፈት ቤት ቀርበው በመመዝገብ በቅደም ተከተላቸው እንዲሁም ቀድሞው በግንባታ ውስጥ ይሳተፉ የነበሩ ተቋራጮች የጀመሩትን ሥራ በሚያገባድዱበት ጊዜ አፈፃፀማቸውን መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲሰማሩ ይደረጋል፡፡ ሆኖም ይህ አሰራር የሚመራበት እራሱን የቻለ መመሪያ ያልተዘጋጀለት በመሆኑ ተቋራጮች ለመመልመል የተዘጋጀን የመመዘኛ መስፈርት በመጠቀም እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ይህም አሰራሩ ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲጎድለው በማድረግ በአንዳንድ ፕሮጀክቶች ከደላሎች ጋር በመመሳጠር «ሥራ እንድታገኙ ማድረግ እንችላለን» በሚል ያልተገባ የጥቅም ትስስር እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡
ለአብነትም « በ2008 በጀት ዓመት የህንፃ ተቋራጮች የሥራ ምደባ አሰራርን አስመልክቶ በተቋሙ በተሰራ የክዋኔ ኦዲት በወቅቱ በህንፃ ግንባታ ሥራ ላይ ከተሰማሩ 658 ተቋራጮች መካከል 105 የሚሆኑት በተመሳሳይ ወቅት ሊገነቡት ከሚገባቸው ህንፃ በላይ እንዲገነቡ ሥራ የተሰጣቸው መሆኑን አረጋግጠናል» በማለት ጠቅሰዋል፡፡
የኮንዶሚኒየም ቤቶች ተገንብተው ሲጠናቀቁ ወይም ግንባታቸው ከ80 በመቶ በላይ ሲደርስ ዕጣ እንዲወጣባቸው ለቤቶች ማስተላለፍና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት እንደሚተላለፉ ቢታወቅም አብዛኛውን ጊዜ ዕጣ እንዲወጣባቸው የሚተላለፉ ቤቶች የሚገኙበት የግንባታ ደረጃ በዕጣ ለዕድለኞች መተላለፍ በሚችሉበት ደረጃ ላይ ስለመድረሳቸው በቅድሚያ በአግባቡ ሳይረጋገጥ የሚተላለፍበት ሁኔታ መታየቱን አቶ ወንድይራድ ያመለክታሉ፡፡ በተለይም ቀሪ የሳይት ወርክ ሥራዎችን እያሉ፣ የተከማቸ አፈር ሳይነሳ፣ የጋራ መጠቀሚያ ህንፃዎች፣ የፍሳሽና የኤሌክትሪክ መስመሮች ሳይጠናቀቁ በተጨማሪም በተላለፉ ቤቶች ላይ የተሰረቁ እቃዎች እንዲሟሉ ሳይደረግ እና መሰል ችግሮች ባሉበት ሁኔታ ዕጣው ለወጣላቸው ዕድለኞች ቤት የሚተላለፍበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህም ዕጣ የደረሳቸው ዕድለኞች ፈጥነው በየደረሳቸው ቤት ለመገልገል እንዲቸገሩ ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም የቤቱ ማጠናቀቂያ ጊዜ በተራዘመ ቁጥር ዕጣው የወጣላቸው ግለሰቦች በቤቱ ሳይገለገሉ ያላአግባብ ከባንክ ጋር የብድር ወለድ እንዲከፍሉና ለተጨማሪ ወጪ የሚያደርግበት ሁኔታ መፈጠሩን ያስረዳሉ፡፡ በሌላ በኩልም ግለሰቦች ካለባቸው የመኖሪያ ቤት ችግር አንፃር በራሳቸው ወጪ የተጓደሉ እቃዎችን የሚያሟሉበት ሁኔታ በመኖሩ በአንዳንድ ሥነምግባር የጎደላቸው ሠራተኞች በቤቱ ስም እቃዎችን ወጪ በማድረግ ለግል ጥቅም እንዲውሉ በር ከፍቶላቸዋል፡፡
እንደ አቶ ወንድይራድ ማብራሪያ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በርካታ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች ከመሃል ከተማ ለልማት ሥራ እንዲነሱ ሲደረግ፤ ቀደም ሲል የቀበሌ ቤት ይሰጥ የነበረ ሲሆን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የቀበሌ ቤት በመልሶ ማልማት ምክንያት የሚፈርስ በመሆኑ የቀበሌ ቤት እጥረት በከተማው ውስጥ እያጋጠመ ይገኛል፡፡ በአንፃሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች በመሃል ከተማ የሚገኙ በመሆኑና በመልሶ ማልማቱ ምክንያት እንዲነሱ ሲደረግ በ10/90 ፕሮግራም ለመሳተፍ ክፍያውን ለመፈፀም የአቅም ውስንነት ያጋጥማቸዋል፡፡ ይህም የተጎሳቀለውን የከተማዋን ገፅታ በመልሶ ማልማት ለመቀየር በመንግሥት የተጀመረውን እንቅስቃሴ ከተያዘለት የጊዜ ገደብ በላይ እንዲራዘም በማድረግ ለቤቶች ግንባታ የሚያዝን በጀት እንዲጨምር አድርጓል፡፡ የቅድመ ክፍያውን እንኳን ከፍለው ዕጣ የወጣላቸው ዕድለኞች «ቀሪውን ክፍያ መክፈል አልችልም» በሚል የተሻለ አቅም ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በሽያጭ የሚያስተላልፉ በመሆኑም በፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳረፍ በመንግሥት አሰራር ላይ ህብረተሰቡ እሮሮ እንዲያነሳ ምክንያት ሆኗል፡፡
በወቅቱ ያልተሰበሰቡና ያልተከፈሉ ሂሳቦችም በፕሮጀክቱ በስፋት እንደሚስተዋል አቶ ወንድይራድ የኦዲት ሪፖርትን መነሻ አድርገው ይጠቁማሉ፡፡ ከተገኙ ግድፈቶች መካከልም የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ላይ ከተደረገ ኦዲት በተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳቦች ላይ የሚደረግ ክትትልና ቁጥጥር የተጠናከረ አለመሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
«የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ የነበሩ ተቋራጮች 1ሚሊዮን 518ሺ 556 ብር ክፍያ ወስደው ሥራቸውን በማቋረጣቸውና በሌሎች ምክንያቶች ያልተመለሰ ገንዘብ ህግ ክፍል ተልኮ ክትትል እየተደረገበት መሆኑን በኮሚሽኑ በተደረገው ማጣራት ተደርሶበታል» ይላሉ፡፡በተጨማሪም የሚኪሊላንድ ሳይት በማዕከል ተጀምሮ ኮልፌ ቀራንዮ እንዲያጠናቅቀው የተሰጠው ግንባታ ላይ ከኮንትራክተሩ የተቀነሰ የማቴሪያል ዋጋ በወቅቱ ያልተከፈለ ሂሳብ 10ሺ 322 ብር በማዕከል መፍትሄ እንዲሰጥበት በደብዳቤ ተጠይቆ መልስ እየተጠበቀ እንደሚገኝ ያመለክታሉ፡፡
በማንኛውም የቅድመ ክፍያ ወይንም አገልግሎት ለማግኘት የሚፈፀሙ ክፍያዎች ላይ ተገቢ የሆነ የቅርብ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን መንግሥት ማህበራትን ለማበረታታት የሚሰጠው ቅድመ ክፍያን በተመለከተ ሥራውን ጀምረው ጥለው የሚጠፉ ወይም አቋርጠው የሚሄዱበት፣ የሚበተኑ፣ አድራሻቸው የማይታወቅ፣ ከሀገር ውጭ የወጡ ዜሮ ወይም ኔጌቲቪ ባላንስ ሲሆንባቸው ለማይወጡ ማህበራት ደብዳቤ በመፃፍና በተለያዩ ዘዴዎች በመጥራት ክፍያ የማይጠየቅበት ሁኔታ ቢኖርም አድራሻቸውን ማግኘት ያልተቻለበት ሁኔታ እንዲሁም አልፎ አልፎ የውል ክፍተት በሚኖርበት ጊዜ በተለይ የተበተኑ ማህበራቶች ተሰብሳቢ ሂሳብን የማይመልሱበት አጋጣሚ ታይቷል፡፡
ለዚህም አብነት የሚያደርጉት ዋሸራ ኮንስትራክሽን ሲቪል ማሽነሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሲሆን፤ ድርጅቱ ካለበት 107 ሺ601 ብር ዕዳ ውስጥ 33ሺ 339 የመለሰ መሆኑንና 74 ሺ 261 ብር ግን ለመመለስ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ክስ እንዲመሰረት ለህግ ክፍሉ የቀረበ ከመሆኑ ባለፈ የተወሰደ ተጨባጭ እርምጃ አለመኖሩን ነው የሚያስረዱት፡፡
በሂሳብ አመዘጋገብ አሰራር ላይም ክፍተት የሚስተዋል መሆኑን በኮሚሽኑ ምርመራ መታወቁን ይጠቀማሉ፡፡ በተለይም የተሰብሳቢ ሂሳብ እንቅስቃሴ በእለቱ በሂሳብ መዝገብ ላይ መመዝገብና በሂሳብ ሌጀር ላይ መወራረስ እንዳለበት ቢታወቅም በተቋሙ ከሚንቀሳቀሰው ከፍተኛ የገንዘብ መጠን አኳያ የመደበኛ አካውንትና የግንባታ አካውንት ሂሳቦችን በመለየት ራሱን የቻለ የክትትል ባለሙያ ያልተመደበለት ሁኔታ ታይቷል፡፡ በጥቅል ገቢና ወጪ ሂሳቦች ባለሙያዎች እንዲከታተሉ በመደረጉም ሂሳቦችን በአግባቡ ከማስተዳደር አኳያ ክፍተት ይስተዋላል፡፡ ይህንንም በኮልፌ ቀራንዮ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ላይ የተደረገ የኦዲት ግኝቶች መሰረት በማድረግ ኦዲት በተደረገበት ወቅት 33ሚሊዮን 897ሺ 728 ብር የተሟላ መረጃ ባለመቅረቡና ተቀፅላ ሌጀር ባለመኖሩ ተሰብሳቢ ሂሳቡን ማጣራት ያልተቻለበት ሁኔታ የነበረ መሆኑና በኦዲት በተሰጠው አስተያየት መሰረት አድርገው ነው የጠቀሱት፡፡
እንደአቶ ወንድይራድ ማብራሪያ፤ የከተማ አስተዳደሩ በእቅድ ለያዛቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ የሚያስፈልግ ግብዓት በተመለከተ መቼ? ምን? ከየት? እንዴትና ለማን? እንደሚገዛ በሚገልፅ የግዥ እቅድ መሰረት በኃላፊነትና በተጠያቂነት መንፈስ ሊከናወን እንደሚገባ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን በግንባታው ሂደት እንዲማከሩ የሚቀጠሩ አማካሪ መሐንዲሶችን ተጠያቂ ከማድረግ አኳያ የተዘረጋው የቁጥጥር ስርዓት የተጠናከረ ባለመሆኑ አልፎ አልፎ በአንዳንድ አማካሪ መሐንዲሶች የሚያዘጋጁት የግንባታ ግብዓት መጠን ለግንባታው ከሚያስፈልግ መጠን በላይ ወይም በታች የሚሆንበት ሁኔታ በስፋት ታይቷል፡፡ የግንባታው ግብዓት የሚገዛበትን ትክክለኛ ጊዜም በወቅቱ አዘጋጅቶ ለግዥ ክፍል አይቀርብም፡፡ አንዳንድ የግንባታ ቦታዎች ለግንባታው ከሚያስፈልግ ግብዓት በላይ ዕቃዎች ተገዝተው ለብክለት የሚዳረጉበት ሁኔታ አለ፡፡ በሌሎች የግንባታ ቦታዎች ደግሞ የግብዓት አቅርቦት ግዥ የማይፈፀም ከመሆኑም በተጨማሪ በግብዓት እጥረት ምክንያት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ የማይጠናቀቁበት ሁኔታ አጋጥሟል፡፡
የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ አጦ በበኩላቸው፤ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በመንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከሚገነቡ ተቋማት መካከል መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ መንግሥት በሰጠው ትኩረት ልክ ሥራው በፍጥነት በጥራት እና ከሙስና በፀዳ መልኩ ተሰርቶ ለተጠቃሚው ህብረተሰብ እንዲሸጋገር ማድረግ እንደሚጠበቅም ያመለክታሉ፡፡
ከዚህ አኳያ በፕሮጀክቱ ላይ ኮሚሽኑ ያደረጋቸው ተደጋጋሚ ጥናቶች ዘርፉን ለሙስና ብልሹ አሰራር እያገለጡ ያሉ 18 ቁልፍ ችግሮች መለየታቸውን አስታውሰው፤ «በጥናቱ እንደማሳያ ያቀረብናቸው ችግሮች በጣም አፋጣኝ እርምጃ ሊወሰድባቸው የሚገቡ ናቸው» ይላሉ፡፡ በተለይም የመጨረሻ ዳኞችን ህዝብ እንደመሆኑና እየፈሰሰ ያለውን ከፍተኛ የአገር ሀብት እንደመሆኑ ዜጎች በታሰበው ልክ ተጠቃሚ ካልሆኑ ጦሱ አሁን ካለውም በላይ የከፋ ይሆናል የሚል ስጋት አላቸው፡፡
እንደእርሳቸው እምነት፤ ጥናቱ ውጤታማ የሚሆነው ግኝቶች በትክክል መሬት ላይ ማረፍ ሲችሉ ነው፡፡ ምንም እንኳን የክስና ምርመራ ሥራ ወደ ፌዴራል ዓቃቢ ህግ የተላለፈ ቢሆንም በቅንጅት የሚሰራ በመሆኑ ወደ ወንጀል የሚያመራ ጉዳይና ተጠያቂነት የሚከተልባቸው አሰራሮች ፖሊስ እንዲመረምረው ይደረጋል፡፡
አቶ ሃረጎት አለሙ የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራአስኪያጅ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ጽሕፈት ቤቱ ከኮሚሽኑ ጋር በጋራ ለበርካታ ዓመታት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ኮሚሽኑ ያደረገው ጥናት መሬት ላይ በተጨባጭ የሚታዩና ጽሕፈት ቤቱም ከዚህ ቀደም የሚያውቃቸው ናቸው፡፡ መርሐ ግብሩ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ካመጣው አወንታዊ ሚና ባሻገር በዚያው ልክ አጠቃላይ የኮንስትራክሽን የሙስና ተጋላጭነቱ እያደገ መምጣቱን ያመላክታል፡፡ ጥናቱ በቀጣይ ለሚሰሩ ሥራዎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡
ይሁንና ችግሩ ከተገለፀውም በላይ የሰፋ እንደሆነ አቶ ሃረጎት ያምናሉ፡፡ በተለይም ከግብዓት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ያለው ችግር ከፍተኛ እንደሆነ ነው የሚገልፁት፡፡ «ጽሕፈት ቤቱ ሥራውን ሲጀምር ከነበረው በላይ አሁን ላይ በአቅምም በልምድ እያደገ ቢመጣም የግብዓት አቅርቦት ሥርዓት፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ትልቁ ችግራችን ሆኖ ቀጥሏል» ይላሉ፡፡ የህብረተሰቡን ፍላጎት ሊያሟላ በሚችል መልኩ የሚታዩ ጉድለቶች አሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ከ550 በላይ ግብዓቶችን እየገዛ ያቀርባል፤ በዚህ የግብዓት ግዢ ሰንሰለት በርካታ የተንዛዙና ለብልሹ አሰራር ተጋላጭ የሆኑ አካሄዶች አሉ፡፡
ይህንን ከመቆጣጠር አኳያ የከተማ አስተዳደሩ በራሱ መንገድ ጥናት አጥንቶ የአሰራር ሥርዓቶችን ለመዘርጋት ጥረት እያደረገ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ «ከዚህ በላይ ተቋሙ ተልዕኮውን ሊሸከም በሚችል ደረጃ ያለበት ችግሮች በጥናት ተረጋግጠው ቀጣይ መፍትሄ ለማስቀመጥ ታስቧል፡፡ በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ ለመፍታት አቅጣጫ ተቋምጧል» ይላሉ፡፡ በኮሚሽኑ የተደረገው ጥናት አስተዳደሩ ለሚያደርገው ጥረት የበለጠ ጠቃሚ ግብዓት እንደሚሆን ነው ያስረዱት፡፡
ከሥነምግባር ጋር በተያያዘ የሚታዩ ችግሮችን ከመፍታት በተለይም የተጠያቂነት አሰራርን ከመዘርጋት አኳያ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ለአብነት ያህልም «ከኮሚሽኑ ጋር በመተባበር በ2008ዓ.ም በተደረገው ጥናት መነሻነት በተካሄደው የኦዲት ምርመራ ከ189 ሚሊዮን ብር በላይ ተመላሽ አድርገናል» ይላሉ፡፡ አላሰራ ያሉ ተቋማትንም የአደረጃጀት ማስተካከያ መደረጉን ጠቁመው፤ ይሁንና አሁንም ቢሆን ክፍተቱ ሰፊ በመሆኑ ስርነቀል የሆነ ለውጥ ለማምጣት ሰፊ ሥራ እንደሚጠይቅ እርሳቸው ያምናሉ፡፡

ማህሌት አብዱል

 

 

 

Published in ፖለቲካ

 ብዙ ከተሞችን አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን አፈሯን ከረገጡበት ቅፅበት አንስቶ ውስጣዊ መረጋጋትን አብዝታ የምትቸር ከተማ አክሱም ትመስለኛለች፡፡ አንዳንድ ከተሞች ምሽታቸው ከውሏቸው ብዙ አይለይም፡፡ ቀን ጫጫታ፤ ምሽት ጫጫታ፡፡ በእርግጥ እንዲህ አይነቱን የከተሞች ባህሪ የሚወዱ ሰዎች የመኖራቸውን ያህል ፀጥታን የሚናፍቁም አያሌ ናቸው፡፡ የአክሱም ከተማ ዝምታ ውስጥ ታሪክ መስካሪ፣ ጥንትን ዘካሪ እውነት አለ፡፡ የከተማዋ ምሽቶች ከውሎዋ ብዙ አይለይም፡፡ ሁለቱም መሰረታቸው ፀጥታና እርጋታ ነው፡፡ 

ጎብኚዎች የእርጋታዋን ሚስጥር ከብዙ ነገር ጋር ያዛምዱታል፡፡ አንደኛው መንፈሳዊነቷን ሲያነሳ ሌላኛው ጥንታዊነቷ ውስጥ የተጠራቀመው ታሪክ የሰጣት ገፅታ እንደሆነ ይገምታል፡፡ ጎልማሳው አቶ ሰለሞን ጣሰው በስራ ምክንያት ሰሞኑን ወደ ከተማዋ ጎራ በማለት ከሳምንት በላይ ቆይቷል፡፡ ለእርሱ በሕይወት ዘመኑ እጅግ ከሚናፍቃቸው ከተሞች አንዷ አክሱም ነች፡፡ ይሄ የስራ አጋጣሚ እያመሰገነ በአደባባዩ ዙሪያ ከሀውልቶቹ ግርጌ ምስሉን በተንቀሳቃሽ ስልኩ ለታሪክ ያስቀራል፡፡
‹‹ሁሌም ላያት እጓጓ ነበር›› ሲል ንግግሩን የሚጀምረው አቶ ሰለሞን፤ ወደ ታሪካዊ ስፍራዎች ጎራ ሲል ኢትዮጵያዊነቱ እንደሚጎላና በታሪኩ እንደሚኮራ ይገልጻል፡፡ ጠጋ ብዬ ‹‹አክሱም ምኗ መሰጠህ?›› ስል ጠየኩት፡፡ ምላሹ ፈጣንና ቀልጣፋ ነው፡፡ ‹‹ታሪኳ እና ዝምታዋ›› አለኝ፡፡ ታሪክን የመመርመር ዝንባሌ አለው፡፡ የጉብኝቱ ጥልቅ ተመስጦም ከታሪክ መፅሐፍ ገፆች ያገኛቸውን ክስተቶች በዓይኑ ከሚመለከታቸው ሐውልቶች ጋር የሚያነፃፅር አስመስሎታል፡፡
እንደ አቶ ሰለሞን ሁሉ፤ ጥቂት የማይባሉ የውጭና አገር ውስጥ ጎብኚዎች በጥንታዊቷ አክሱም ጽዮን ማርያም ቤተክርስቲያን ደጃፍ እንዲሁም ሻገር ብለው በግርማ ከቆሙት የአክሱም ስልጣኔ ምልክቶች ስር ምስላቸውን ያስቀራሉ፡፡ ተንቀሳቃሽ ስልካቸው ስራ በዝቶበታል፡፡ በስልክ ያልበቃቸው ደግሞ እንደ ወጣት ዳዊት ላሉት ፎቶ አንሺዎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ እኔም በዚህ ስፍራ ተገኝቼ የእነዚህን ወጣቶች ስሜት ሳልጋራ መመለስ አልፈለኩም፡፡
ከአንደኛው ጎብኚ ፊት ያበራው ‹‹ፍላሽ›› በቅጡ ሳይጠፋ ሌሎች ጎብኚዎችን ከሚያማትረው ወጣት ጠጋ ብዬ አወጋሁት፡፡ ወጣቱ ዳዊት አብርሃ ወልዴ ይባላል፡፡ በማኔጅመንት ትምህርት ዲፕሎማ ቢኖረውም ባለፉት ስድስት ዓመታት በላይ አክሱምን ሊጎበኙ ጎራ የሚሉ እንግዶችን ፎቶ በማንሳት ይተዳደራል፡፡ የአክሱም ከተማ የቱሪስት ፍሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል ቢያሳይም ዘርፉን በማስተዋወቅ በኩል አሁንም ብዙ መስራት ይጠይቃል፡፡
‹‹እንግዶች ሲመጡ በቅልጥፍና የማስተናገድ ልምድ ይጎላል›› የሚለው ወጣቱ የፎቶ ባለሙያ፤ በዚህም ከአገር ውስጥም ይሁን ከባህር ማዶ ከሚመጡ ጎብኚዎች ማግኘት የሚቻለው ገቢ እንዳያድግ ማነቆ ሆኗል፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በመንፈሳዊ ጉዞ ተሰባስበው አክሱም የሚመጡ ተጓዦች እየተበራከቱ ይገኛሉ፡፡ ይሄም ለከተማዋ ከሚያመጣው ተጨማሪ ገቢ ባሻገር የአገር ውስጥ ጉብኝት ባሕል ከማዳበርም አንፃር ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ ነገር ግን ይላል ወጣቱ፤ እንዲህ አይነቱን መልካም አጋጣሚ ሳይቀዛቀዝ ለማስቀጠል በማስተዋወቁ ይሁን በመስተንግዶው ቀልጣፋ መሆን ይጠይቃል፡፡
አክሱም ስትጠቀስ በብዙዎች አዕምሮ ቀድሞ የሚከሰተው የአክሱም ዘመን ስልጣኔን የሚመሰክሩትና የሚያስተዋውቁት ግዙፍ ሀውልቶች ብቻ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን አክሱም ቆመው ከሚታዩት ሐውልቶቿ በታች ያልተነገሩ በርካታ ሚስጥሮችን በውስጡ አቅፋ ለዘመናት ቆይታለች፡፡ ለአብነትም በዘመኑ የተሰሩ 12 መቃብሮች በአንደኛው ሐውልት ስር ከሚገኝ ጨለማ ክፍል ይገኛሉ፡፡ የመተላለፊያዎቹ ጥበት የላሊበላን የውስጥ ለውስጥ መሿለኪያዎች ያስታውሳሉ፡፡ ከተጠቀሱት ጥንታዊ መቃብሮች መካከል 10 በቁፋሮ ሲገኙ ቀሪዎቹ ሁለቱ ግን ገና ቁፋሯቸው እንዳልተጀመረ አስጎብኛችን ነግረውናል፡፡
የሐውልቶቹ አስጎብኚ አቶ መኮንን ገብረመስቀል፤ ከተቆፈሩት መቃብሮች ውስጥ የሰውና የእንስሳት ቅሬት አካል ጨምሮ ወርቅ፣ ጥንታዊ የመገበያያ ገንዘቦች እንዲሁም የተለያዩ ጥንታዊ ቅርሶች ተገኝተዋል፡፡ እነዚህ ቅርሶች የተገኙበት ምክንያት አስጎብኚው ሲያብራሩ በዘመኑ ‹‹ከሞት በኋላ ሕይወት አለ›› ብለው ያምኑ ስለነበር ከነንብረታቸው ይቀበሩ ስለነበር ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ የንጉሱ ቤተሰቦች መቃብር ውስጥ የነበሩ በርካታ ቅርሶች በ1974 ዓ.ም ተዘርፈው ወደ ተለያዩ አገሮች መውጣታቸውን ይገልጻሉ፡፡
ሐውልቶቹ ከአንደኛው መቶ እስከ አስረኛው መቶ ክፍለ ዘመን በነበረው ስልጣኔ የተተከሉ ናቸው፡፡ የአክሱም ሐውልቶች በይበልጥ ገዝፈው የሚታወቁት በከተማዋ አደባባይ የሚገኙት ናቸው፡፡ በዚህ ስፍራም ጣሊያን ዘርፋ የወሰደችውና በሮም የተከለችው በኋላም በብዙ ድርድር ወደ አገሩ የተመለሰው ሐውልትም ቆሞ ይገኛል፡፡ ብዙ ጎብኚዎች በከተማዋ የሚገኙት እነዚህ ሐውልቶች ይመስሉታል፡፡ አስጎብኚው አቶ መኮንን እንደሚሉት ግን፤ በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች አንድ ሺ 30 ሐውልቶች ተተክለው ይገኛሉ፡፡ አንደኛው የማስተዋወቅ ክፍተት መኖሩ የሚታየውም ከዚህ አንፃር ነው፡፡
በተለያዩ የከተማው አካባቢዎች የሚገኙት በርካታ ሐውልቶች በሦስት ይከፈላሉ፡፡ በቁመት ዘለግ ብለው የሚታዩት የንጉሳውያን ቤተሰቦች መቀበሪያ ናቸው፡፡ መለስተኛዎቹ ለባለፀጎች እንዲሁም አጫጭር የሚባሉት የአገልጋዮች መቃብር እንደሆኑ ይታመናል፡፡ ከሐውልቶቹ መካከል አንደኛው በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ እንደወደቀ የሚነገረውና አሁንም ወድቆ የፈራረሰው ግዙፍ ሐውልት ተጠቃሽ ነው፡፡ ቁመቱ 520 ቶን ክብደት ሲኖረው 33 ነጥብ አምስት ሜትር ይረዝማል፡፡
አደባባዩ ላይ የቆሙት ሐውልቶች ንጉስ ኢዛና በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የክርስትና ሀይማኖትን እስኪቀበል ድረስ ንጉሱ ይከተል የነበረውን የፓጋን እምነት የሚወክሉ እንደነበሩ አስጎብኚያችን ይገልጻሉ፡፡ ከዚያም በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ንጉሱ ክርስትና እምነት ሲቀበል ከሐውልቶቹ ፊትለፊት ማሪያም ጽዮን ቤተክርስቲያን አሰርቷል፡፡ ቤተክርስቲያኗ በየጊዜው ማስፋፊያ የተደረገላት ቢሆንም በዮዲት ጉዲት እና በግራኝ መሐመድ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ደርሰውበታል፡፡
የአክሱም ሐውልትም ሆነ የማሪያም ጽዮን ቤተክርስቲያን ለአገርም ይሁን ለከተማዋ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ መኮንን፤ ቅርሶቹን ከቱሪዝም ገቢ ባሻገር የትናንት ታሪክ ለነገው ትውልድ ለማሻገር ሦስት ጉዳዮች ትኩረት ይፈልጋሉ፡፡ ጥበቃ፣ ጥገና እንዲሁም ማስተዋወቅ የሚሉት ናቸው፡፡ ጎብኚዎችን በተመለከተ ‹‹ከዜሮ አንድ ይሻላል›› የሚሉት አስጎብኚው፤ በተለይ ለአክሱም ጽዮን ዓመታዊ ንግስ እንዲሁም በተማሪዎች የአገርን እወቅ ጉዞዎች ዘርፉ መነቃቃት ጀምሯል፡፡
የአስጎብኚውን ሃሳብ የሚያጠናክሩት የከተማዋ ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረመድን ፍፁምብርሐን ‹‹ፍሰቱ በየጊዜው እድገት ቢኖርም አሁንም የሚጠበቀውን ያህል አይደለም›› ይላሉ፡፡ ስፍራዎቹን በማስተዋወቅ በኩል ብዙ የሚጠበቅ የቤት ስራ አለ፡፡ ከተማዋ በአብዛኛው ጎብኚዎች የምትታወቀው በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሣይንስና የባሕል ድርጅት(ዩኔስኮ) በተመዘገበው የአክሱም ሐውልት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ውስጧን ይበልጥ ዘልቆ ላስተዋላት ከአክሱም ሐውልት በተጨማሪ መጎብኘት ያለባቸው 11 ታሪካዊ ስፍራዎች ባለቤት ናት፡፡
አክሱም የኢትዮጵያን ታሪክና ገናናነት የምታመላክት ጥንታዊ ከተማ ናት፡፡ ነገር ግን በዚህ የታሪክ ርቀት ልክ የሚሰፈር ዕድገት ላይ አለመሆኗን በተለያየ መልኩ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ‹‹ከተማዋ የስሟን ያህል አላደገችም›› የሚሉት አቶ ገብረመድን፤ በተለይም በልማት ረገድ ብዙ መስራት ይጠይቃል፡፡ ይሄን ስራ ከሚደግፉ የገቢ ማስገኛ ዘርፎች መካከል ደግሞ ቱሪዝም ቀዳሚው በመሆኑ አሰራሩ በአግባቡ መፈተሽ አለበት፡፡
ከተማዋ ባለፈው ዓመት 12ሺ የሚሆኑ የባህር ማዶ ጎብኚዎችን ማስተናገዷን ይናገራሉ፡፡ በተያዘው ዓመት ሰባት ወራት ደግሞ 16 ሺ የሚሆን የባህር ማዶ ጎብኚ አክሱም ከተማ ጎራ ብሏል፡፡ በገንዘብ ሲተመን የዘንድሮው ገቢ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ይሄ የጎብኚዎች ቁጥርም ሆነ የተገኘው ገቢ በየጊዜው መሻሻሉን ያሳያል የሚሉት የፅሕፈት ቤት ኃላፊው፤ ካሉት ቅርሶች ብዛት አንፃር ግን ቁጥሩ በቂ አይደለም፡፡
የቱሪዝም ዘርፍ ቀዳሚ ተጠቃሚ ማድረግ የሚገባው የአካባቢውን ማሕበረሰብ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አክሱም ውስጥ በርካታ ወጣቶች ከቱሪዝም ቁሳቁስ ጋር በተያያዘ በርካታ ምርቶችን ወደ ገበያ ቢያቀርቡም በተደራጀ መልኩ አይደለም፡፡ አብዛኞቹ ወጣቶች የጎብኚዎችን ኮቴ እየተከተሉ በመሸጥ ራሳቸውን ይደጉማሉ፤ ቤተሰብም ያስተዳድራሉ፡፡ ነገር ግን ይሄ የወጣቶቹ ጥረት በተደራጀ መልኩ ቢሆን ገቢያቸውም በዚያው ልክ ያድጋል፤ ለገፅታ ግንባታም መልካም ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
በዚህ ረገድ ምን አስባችኋል? ያልናቸው አቶ ገብረመድን ‹‹ወጣቶችን በማደራጀት በኩል የተሰሩት ስራዎች አሉ፤ ነገር ግን ስራዎቹ ገና ጅምር ላይ ያሉ ናቸው›› በማለት ቀጣይ ስራቸው መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ለአብነትም በስጦታ ዕቃዎች አቅራቢነት የመሸጫ ቦታ ተሰጥቷቸው የሚሰሩ 20 ወጣቶች ቢኖሩም ይሄ ቁጥር ከከተማዋ ወጣት ቁጥር ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ በመሆኑም የወጣቶች ስራ ዕድልን ከቱሪዝም ዘርፉ ማገናኘት ጊዜ የማይሰጠው የቤት ስራ መሆኑን መገንዘብ የግድ ይላል፡፡

ብሩክ በርሄ

Published in ኢኮኖሚ

በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2018 መባቻ የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሙሐሙዱ ቡሃሪ ‹‹ቦኮሃራም አክትሞለታል!›› ሲሉ ነበር የገለጹት፡፡ የፕሬዚዳንቱ መግለጫ ለምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ዜጎች ብቻ ሳይሆን ለቀጣናውም ከዜና በላይም ብስራት ነበር፡፡ እ.አ.አ 2009 ከናይጄሪያ አልፎ በቀጣናው እስላማዊ አክራሪነትን ለማስፋፋት ፀረ ስልጣኔ አቋምን አንግቦ ብቅ ያለው የሽብር ቡድን በተለያዩ ጊዜያት ታዳጊ ሴቶችን በማፈን ለብዙ ወላጆች የጭንቀት ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ታጣቂ ቡድኑ ከእኩይ ተግባሩ ባሻገር በተለይ በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ በፈፀማቸው ተደጋጋሚ ጥቃቶች ከ20 ሺ በላይ ዜጎችን ገድሏል፡፡ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑትን ደግሞ ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል፡፡

ከቦኮሃራም ተደጋጋሚ ጥቃት ጋር በተያያዘ ‹‹የናይጄሪያ መንግሥት ለዜጎቹ ደህንነት ዋስትና መስጠት ተስኖታል›› በሚል የሚሰነዘረው ትችትም ተጠናክሮ ቆይቷል፡፡ ትችቱ በቀድሞ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን እንዲሁም በአሁኑ ቡሃሪ ላይ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሰነዘር ነው፡፡ የአገሪቱን መከላከያ ኃይል ጥቃቱን ሊመክት አለመቻሉ በሕዝቡ ዘንድ ጥርጣሬን ያጫረ ነበር፡፡
እ.አ.አ 2015 በሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ጉድላክ ጆናታንን በማሸነፍ በምርጫ ወደ መንበረ ስልጣኑ ብቅ ላሉት አዛውንቱ ሙሐሙዱ ቡሃሪ በፕሬዚዳንታዊ ቃለመሃላቸው ወቅት በአገሪቱ ከተንሰራፋው ሙስና በማስቀደም የመጀመሪያ ትኩረት የሰጡት ቦኮሃራምን ማዳከም ነበር፡፡ የሽብር ቡድኑን አሽመደምዳለሁ ብለው ነበር፡፡ ቃላቸውን ተከትሎ በአገሪቱ ጦር ኃይል በተወሰዱ ተከታታይና ተደጋጋሚ ጥቃቶች ቡድኑ የተዳከመ ቢመስልም ፕሬዚዳንቱ በጥር ወር ‹‹አክትሞለታል!›› ባሉለት ደረጃ ያለመሆኑን የሰሞኑ ጥቃት መስክሯል፡፡
በአገሪቱ ሙቢ በተባለ ከተማ አካባቢ በመስጊድ ላይ በተሰነዘረው የቦምብ አጥፍቶ መጥፋት ጥቃት በድጋሚ የንጹሃን ሕይወት አልፏል፡፡ የሰኞ ዕለቱን የአጥፍቶ ማጥፋት የቦምብ ጥቃት የዘገቡ መገናኛ ብዙሃን የሟቾቹን ቁጥር ከ27 እስከ 42 አድርሰውታል፡፡ የከተማዋን አጠቃላይ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር እዝራ ሳካዋ ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው፤ ከሟቾቹ በተጨማሪ 56 ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል፡፡ ከሰዓት በኋላ ለፀሎት በሚዘጋጁ በርካታ የሙስሊም ምእመናን ላይ የተፈፀመው ጥቃት ከወራት በፊት በተመሳሳይ ስፍራ ከተፈፀመ ጥቃት ጋር እንደሚመሳሰልም የአገሪቱ ፖሊስ ኮሚሽነር አብዱላሂ ያሪማ ለቢቢሲ ገልጸዋል፡፡ በዚያኛው የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት 50 ሰዎች ሕይወታቸው አልፎ ነበር፡፡
በአካባቢው የቡድኑ የሽብር ጥቃት መደጋገም ጋር ተያይዞ ሁኔታው የተለመደ ቢመስልም የአሁኑ ግን ፕሬዚዳንት ቡሃሪ በአሜሪካ ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ ዋሽንግተን በሚገኙበት ቅፅበት መፈጸሙ ነው፡፡ ከዚህኛው ጥቃት ጋር ባይያያዝም ጉብኝቱን ተከትሎ ቡሃሪ አገራቸው ከአሜሪካ 12 ዘመናዊ የጦር ጀቶች መግዛቷን ገልጸዋል፡፡
ከጉብኝቱ በኋላ ከቡሃሪ ጋር የጋራ መግለጫ የሰጡት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ናይጄሪያ አሁን ከገዛቻቸው ጀቶች በተጨማሪ ዘመናዊ የጦር ኢልኮፕተሮች ግዢም በሂደት ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹አዳዲሶቹ የጦር ጀቶች ናይጄሪያ የሽብር ቡድኖችን ላነጣጠረ እርምጃዋ ተጨማሪ ብቃት ይሰጣል›› ያሉት ትራምፕ፤ አላማውም ንፁሐንን ከጥቃት ለመታደግ ያለመ ነው፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ሃሳባቸውን የሚሰጡ የፖለቲካ ተንታኞች የናይጄሪያና አሜሪካ የጦር መሳሪያ ትብብር የሽብር ቡድኑን ለማዳከም ትልቅ አቅም ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን የፀረ-ቦኮሃራም ዘመቻው በተናጠል እርምጃ ስኬታማ ለማድረግ የማይታሰብ ነው፡፡ ምክንያቱም የሽብር ቡድኑ እስካሁን በአካባቢው የወሰዳቸው ተደጋጋሚ ጥቃቶች ናይጄሪያን ብቻ ሳይሆን የአካባቢውን አገሮች በአጠቃላይ እንቅልፍ የነሳ ሁኗል፡፡
ለአብነትም እ.አ.አ 2016 ብቻ ቦኮሃራም ከወሰዳቸው 307 አጠቃላይ ጥቃቶች 189 ያህሉ ያነጣጠሩት በናይጄሪያ ሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች ነው፡፡ ቀሪዎቹ 58 ጥቃቶች በጎረቤት ካሜሮን፣ 35 በቻድ እንዲሁም 25 በኒጀር ላይ የተፈጸሙ ናቸው፡፡ እነዚህ ጥቃቶች እ.አ.አ 2017 በናይጄሪያና ካሜሮን በቁጥር መጨመር አሳይተዋል፡፡ በተቃራኒው በቻድና ኒጀር ቢቀንስም ከሽብር ቡድኑ መዳከም ጋር ተያይዞ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ መኖሩ ተገልጾል፡፡ ቢሆንም ይላሉ ተንታኞች፤ በተለይ በአካባቢው አገሮች መካከል የሚፈጠር አጋርነት ካልተጠናከረ በሽብር ቡድኑ ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎች የታጣቂውን ዕድሜ ለማሳጠር ያዳግታል፡፡
ፕሬዘዳንት ቡሃሪ በዘመነ ትራምፕ ወደ ነጩ ቤት ጎራ በማለት ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች የመጀመሪያው መሪ ናቸው፡፡ ቡሃሪ በጉብኝታቸው ዕቅድ የስደተኞችን ጉዳይ አንዱ አጀንዳቸው እንደሚሆን ተጠብቆ ነበር፡፡ ነገር ግን ፕሬዘዳንቱ እግራቸው ዋሺንግተን ከመርገጡ በአገራቸው መስኪድ ላይ የተፈፀመው ጥቃት የመገናኛ ብዙሐኑንም የትኩረት ነጥብ ወደ ሽብርተኝነት ያዞረ ሆኗል፡፡ ሁለቱም መሪዎች በመግለጫቸው በመጠኑም ቢሆን ግን በስደተኞች ዙሪያ ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡
ዘመናዊዎቹን 12 የጦር ጀቶች ለመግዛት 496 ሚሊዮን ዶላር ቼክ ላይ የፈረሙት ቡሃሪ፤ ግዢው ናይጄሪያ ቦኮሃራምን ለማጥፋት የምታደርሰውን ጥቃት ይደግፋል፡፡ ለዚህም የትራምፕ መንግስት ያሳየውን አብሮነት አድንቀዋል፡፡ የአሜሪካ መከላከያ ለናይጄሪያ ሰራዊት የሚሰጠውን ወታደራዊ ስልጠና ያነሱት ፕሬዘዳንት ቡሃሪ፤ አሜሪካ በዓለምአቀፍ ደረጃ ለምታደርገው የተደራጀ ፀረ-ሽብር ዘመቻ ያሳየችውን ቁርጠኝነት በተጨባጭ ከሚያረጋግጡ አገሮች አንዷ አገራቸው መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህም ምስጋናና አድናቆታቸውን ለግሰዋል፡፡
የአልጀዚራው አህመድ ኢድሪስ ከናይጄሪያ መዲና አቡጃ እንደዘገበው ቡሃሪ ወደ አሜሪካ ተጉዘው የፈፀሙት የጦር መሳሪያ ግዢ ስምምነት ሌላም አላማ እንዳለው ጠቅሷል፡፡ በተለይም ፕሬዘዳንቱ ቦኮሃራምን በመዋጋት በኩል ያሳዩትን ድክመት በመጥቀስ ከተቀናቃኞቻቸው የሚነሳውን ትችት ለማለዘብ ጭምር ያለመ ነው፡፡ ምክንያቱም ይላል፤ የ75 ዓመቱ ቡሃሪ በቀጣዩ ዓመት በሚደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለመወዳደር ዕቅድ ይዘዋል፡፡ ሆኖም ከቦኮሃራም በተጨማሪ ፕሬዚዳንቱ ከጤና አንፃር የሚታይባቸው ተደጋጋሚ ፈተና ለዳግም ምርጫ እንዳይወዳደሩ ዳርጓቸዋል ሲሉ ተቺዎቻቸው ይሞግታሉ፡፡
ከሞጋቾቹ አንዱ የሆኑትና የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኦሊሴንጎ ኦባሳንጁ ለቡሃሪ በፃፉት ደብዳቤ ለሁለተኛ ጊዜ ለመመረጥ የሚያስችል ቁመና ላይ አለመሆናቸውን መግለጻቸውን መገናኛ ብዙሐን ዘግበዋል፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ ለወራት ከስራ ገበታቸው ርቀው ለንደን በሚገኝ ሆስፒታል ህክምና ሲከታተሉ የነበሩት ቡሃሪ ከጤናቸው አሳሳቢነት በተጨማሪ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ያስቀጠሉበት መንገድ ደካማ መሆን የሚያስመርጣቸው አይሆንም፡፡ በዚህ ክፍተት ላይ ቦኮሃራም እያዘናጋ የሚፈፅማቸው ተደጋጋሚ ጥቃቶች ዕቅዳቸውን ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል፡፡
የተለያዩ ተንታኞችና የቀድሞ ፖለቲከኞች የቡሃሪን ዳግም ለመመረጥ ማሰብ ቢቃወሙም የፕሬዚዳንቱ ቃል አቀባይ ፌሚ አዲሲና፤ ትችቱ ለፕሬዘዳንቱ የእስካሁኑ ተስፋ ሰጪ ስራዎች እውቅና ያልሰጠ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ትችቱን በበጎ መልኩ እንደሚወስዱ የሚገልጹት ቃል አቀባዩ፤ ናይጄሪያ በቅርብ ዓመታት ሙስናን በመዋጋት በኩል ያስመዘገበችው ስኬት የቡሃሪ አመራር ውጤት ነው፡፡ እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ የሽብር ቡድኑም ቢሆን ከዚህ ቀደም ከነበረው የከፋ ተፅዕኖ አንፃር መዳከሙን ያሳያል ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
በዚህም ተባለ በዚያ በከፍተኛ ነዳጅ ክምችቷ የጀርባ አጥንትነት በአህጉሩ ቀዳሚ የምጣኔ ሀብት ባለቤት የሆነችው ናይጄሪያ በአንፃራዊ ሰላሟ ውስጥ ኢኮኖሚዋን አረጋግታ ማስቀጠል ችላለች፡፡ አንድ አገር ኢኮኖሚው በአስተማማኝ ሰላም ላይ መሰረት ካላደረገ የተዘራውን በማጨድ በኩል ዘላቂ ዋስትና ማግኘት ግን የሚታሰብ አይመስልም፡፡ የሽብር ጥቃትም ቢሆን አሁን ካለው ዓለምአቀፋዊ ባህሪ አንጻር በአንድ አገር ብቻ ቁርጠኝነት መፍትሄ የሚያገኝ አይሆንም፡፡
በአሜሪካ ጉብኝታቸው ላይ ሆነው ከአገራቸው የተፈጸመውን ጥቃት የሰሙት ፕሬዘዳንት ቡሃሪ ሚሊቴሪያቸውን በጦር መሳሪያ ከማዘመን በተጓዳኝ የጎረቤት አገሮችን አጋርነት ማረጋገጥ ይጠይቃቸዋል፡፡ ለፕሬዚዳንትነት የሚያደርጉት ዝግጅትም አሜሪካን ተሻግሮ ከሚደረግ ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ግዢ ስምምነት አልፎ በፀረ ሽብር ዘመቻ አጋርነትን በመሻት መቃኘት የግድ ይለዋል፡፡

ብሩክ በርሄ

 

Published in ዓለም አቀፍ
Thursday, 03 May 2018 16:43

የተቆጠረ የቤት ስራ

በሀገራችን እየነፈሰ ያለው የለውጥ አየር ዳር እስከዳር በአራቱም ማዕዘናት የሕዝብን ቀልብ በመሳብ ላይ ይገኛል፡፡ ነግሶ የቆየው የሰላም እጦት አለመረጋጋትና መደፍረስ ዛሬ ሙሉ በሙሉ ወደቦታው ተመልሷል፡፡ ይህም ኢሕአዴግ በእርግጥም ጥልቀታዊ ተሀድሶውን በገባው ቃል መሰረት በተግባር ለማዋል እየሰራ ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡
አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በሰዎች የሚመራ እንደመሆኑ መጠን ኃላፊነትን ይዞ ሲሰራ በስራው ሂደት ፈርጀ ብዙ ችግሮች ይገጥሙታል፡፡ በታማኝነት በተለያየ የኃላፊነት ቦታ ያስቀመጣቸው ግለሰቦች የግል ጥቅም እያማለላቸው ሕዝብ ለማገልገል የገቡትን ቃል በመጣስ ሙስና ውስጥ እንደሚዘፈቁ በሕዝቡም ውስጥ የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ችግር እንደሚፈጥሩ በተደጋጋሚ የታየ እውነት ነው፡፡
የተጠቀሱት ችግሮች በአገራችን ላይ ብቻ የተከሰቱ አይደሉም፡፡ ይልቁኑም በቻይና፤ በቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት፤ በኮርያ፤ በምእራቡ አለም፤ በአፍሪካና በኤሽያም ጭምር በተደጋጋሚ እጅግ ስፋት ባለው መልኩ ተከስቷል፡፡ ዛሬም ችግሩ ገዝፎ ይታያል፡፡ ዋናው ቁምነገር ፓርቲዎች ወይም መንግስታት ችግሩን ለመፍታት የሚከተሉት መንገድ ወሳኝ ለውጥ ማምጣት መቻሉ ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም እርምጃዎች አንድም መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጡ፤ አሊያም ሀገር እስከማፈራረስ ማድረስ እንደሚችሉ በቅጡ መገንዘቡ ላይ ነው፡፡
በመንግስትና በሕዝብ ሀብት ላይ በግለሰቦች የሚፈጸም ዘረፋ በሀገር ልማትና እድገት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳድራል፤ ልማትን ያጓትታል፡፡ ሀገር ከድህነት ለመውጣት የምታደርገውን ጉዞ ያደናቅፋል፡፡ ሙስና በብዙ ሚሊዮን ዜጎች ሕይወትና ኑሮ እንዲሁም በሀገር እድገትና ልማት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት እንድትበታተን የምዕራባውያኑ ስውር እጅ የገዘፈ ቢሆንም ሌላኛው መሰረታዊ ምክንያት የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች በከፍተኛ ሙስና ውስጥ መዘፈቃቸው መሆኑ ይታወሳል፡፡ ይሄ ሂደት በመጨረሻ ታላቋን ሀገር ለመፈራረስና ለውድቀት ዳርጓታል፡፡
በቻይናም በፓርቲው ከፍተኛ አመራር ውስጥ ለአመታት የዘለቀው ከፍተኛ ሙስና የአገሪቱን እድገትና ልማት እስከ መግታት ደርሶ ነበር፡፡ በጥልቅ ግምገማና ማጥራት በየደረጃው በወሰዱት ሙስናን የመዋጋትና ሙሰኞችን በሕግ የመቅጣት ወሳኝ እርምጃ ችግሩን አስወግደው ዛሬ ለደረሱበት ታላቅነት በቅተዋል፡፡
በእኛም ሀገር ችግሩ ገዝፎ የተከሰተ ሲሆን አሁን ሕዝቡ የሚጠብቀው ኢሕአዴግ የሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመፍታት የሚወስደውን የማያዳግም ቁርጠኛ እርምጃ ነው፡፡ ሙሰኞችን በሕግ እንዲጠየቁ ከማድረግ ጎን ለጎን የዘረፉትን ንብረትና ሀብት ወደ መንግስትና ሕዝብ ካዝና የመመለስ ሰፊ ስራዎችም እንደሚሰሩ ይታመናል፡፡
ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ዘረፋ ችግር በአምባገነን መንግሥታት፤ በሕዝብ በተመረጡ መንግሥታትና ፓርቲዎች፤ በሪፐብሊካንም ሆነ በዲሞክራት እንዲሁም ሊበራል ነን በሚሉ መንግሥታት ውስጥ ሁሉ የተከሰተ ሲከሰትም የኖረ ችግር ነው፡፡ ለችግሩ እልባት የሚሰጠው ግን በሙሰኞቹ፤ የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ችግር በፈጠሩት መንግሥታዊ አካላትም ሆነ በየደረጃው ባሉ የፓርቲ አመራሮች ላይ በተጨባጭ ማስረጃ ተመርኩዞ በሕግ የሚወሰደው እርምጃ ነው፡፡
ኢሕአዴግ በአዲስ የለውጥ ምእራፍ ላይ ይገኛል፡፡ ቀጣዩ ጉዞ የአዲስ ዘመን ጅማሮ እንደመሆኑ ፓርቲው ከሕዝቡ ተቆጥረው የተሰጡት በርካታ የቤት ስራዎች መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ቀዳሚው የሙስና የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ችግር ደረጃ በደረጃ በመቅረፍ የሕዝቡን መሰረታዊ ችግር መፍታት ነው፡፡ በሀገራችን የተከሰቱት ችግሮች ግዝፈትና ስፋት የተለጠጠ በመሆኑ በብዙ መልኩ ይገለጻል፡፡ በሁሉም መስክ የሚታይ ስር የሰደደ ችግር ስለሆነ በአንድ ግዜ ሁሉንም ችግር መፍታት ይቻላል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ በተጨማሪም የመንግሥትና የሕዝብን የተቀናጀ ርብርብ ይፈልጋል፡፡
ኢሕአዴግ በዋነኛነት ከታዩት ችግሮች በመጀመር በሂደቱ ውስጥ ሕዝቡን በማሳተፍ ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባውም እሙን ነው፡፡ በመላው ሀገሪቱ በአዲስ መንፈስ ብሔራዊ ተነሳሽነትን ያሳየው የሕዝብ እምነትና ተስፋ በዚሁ ሊዘልቅ የሚችለው ኢሕአዴግ ከሕዝቡ ለቀረቡለት ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሽ መስጠት ሲችል ብቻ ነው፡፡ ለዚህም በውስጡ ያሉ ችግሮችን እየፈታ በሙሉ አቅሙ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል፡፡
በእርግጥ ለውጥ የአንድ ጀምበር ስራ አይደለም፡፡ ሂደት ነው፡፡ ሂደቱ ደግሞ ትክክለኛ ጊዜና ቦታ ይፈልጋል፡፡ ሕዝቡ በያለበት ከመንግሥት ጎን በመቆም ሲሰራ ጠንካራ ትብብሩን በተግባር ሲያሳይ የበለጠ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል፡፡
የመንግሥትን በጎ ተነሳሽነትና የመልካም ሂደት ጅምር ማገዝ በስፋት መርዳት ከሁሉም ወገን ይጠበቃል፡፡ ሁሉንም ጉዳይ መንግሥት እንዲያሳካው የሚጠበቅ ከሆነ ውጤት አይገኝም፡፡ ዜጎች በባለቤትነትና በያገባኛል መንፈስ ለተጀመረው ተሀድሶ አጋዥ ሆነው መሰለፍ፤ በየተሰለፉበት የስራ መስክ ተግተው መስራት፤ የተዳከመው ሀገራዊ ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ማድረግ፤ ያለልዩነት ለጋራ ሀገር በጋራ በመቆም መስራት ቀዳሚ ተግባራቸው ሊሆን ይገባል፡፡
በኢኮኖሚና በልማት መስክ ሀገሪቱ ያስመዘገበቻቸውን ታላላቅ ስኬቶች ጠብቆ በመራመድ የበለጡ ከፍተኛ የኢኮኖሚና የልማት ስኬቶችና ድሎች በየመስኩ ለማስመዝገብ እንዲቻል ሁሉም ዜጋ እንደ አንድ ሰው በመሆን ከተንቀሳቀሰ ትልቅ ለውጥ ይገኛል፡፡ ከድሕነት ለመውጣት የተሻለችና የበለጸገች ሀገር ለመገንባት ወሳኙ ስራና ስራ ብቻ ነው፡፡ በላባቸው አሻራ ለትውልድ የሚያልፍ ታላቅ ስራ ሰርተው የሚያኖሩ ሀገርን ሕዝብን ትውልድንም ያኮራሉ፡፡ የሀገርና የሕዝብን ሀብት መዝረፍ በዚህም መነሻነት ሚሊየነር መሆን አንገትን ቀና አድርጎ የሚያደፋፍር ተግባር አይደለም፡፡
በአቋራጭ ያለምንም ልፋት ድካም ውጣ ውረድ በማጭበርበር የመንግስትና የሕዝብን ሀብት ከሙሰኛ ባለስልጣናት ጋር በመመሳጠር እየዘረፉ መክበር በሕዝብ ፊት ውርደትን እንጂ ክብረትን አያስገኝም፡፡ ምንም ሳይለፉ የሀብቱ ምንጭ ከየት እንደሆነ ሳይታወቅ በአንድ ቀን በወራት ባለሀብት ለመሆን የሚቻልባት፤ በአንድ ቀን የግለሰቦች ታሪክ ከምንም ተነስቶ ወደ ኢንቨስተርነት፥ አስመጪ ላኪነትና የድርጅት ባለቤት እንዲሁም ባለብዙ ኩባንያዎች ባለአክሲዮን የመሆን ሂደት መፈተሸ ይገባዋል፡፡ይህ ሁሉ የተዘረፈ የሕዝብ ሀብት ስንትና ስንት ሀገራዊ ችግሮቻችንን በፈታ ድህነታችንን ለመዋጋት እየተሰሩ ላሉት ፕሮጀክቶች በዋለ ነበር፡፡ ስንትና ስንት ክሊኒኮች፤ ጤና ጣቢያዎች በየገጠሩ ጣሪያና ግድግዳ ለሌላቸው ትምህርት ቤቶች ማሰሪያ ማሳደሻ በዋለ ነበር፡፡
በዚሁ በሙሰኞች በተመዘበረው የሀገር ገንዘብ የተጀመረውን ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ለመጨረስ በተቃረብን ነበር፡፡ በሙሰኞች የተበላው የሀገር ሀብት እልፍ ሀገራዊ ቀዳዳዎቻችንን ይደፍን ነበር፡፡ብዙ ነበሮችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ዛሬ የትላንቱን ሳንረሳ ስሕተቱ ዳግም እንዳይደገም እየታገልን የተዘረፉትን የሚቻለውን ሁሉ በማስመለስ መልሶም ወደ ልማት እንዲገቡ ማድረግ የግዴታም ግዴታ ነው፡፡ አስገራሚ የሕዝቡ የመወያያ ርእስ ሆኖ ለአመታት የዘለቀው እልባት የሚሻው የሕዝቡ ጥያቄም ይኸው ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ዳግም በሀገራችን እንዳይከሰት ብርቱ ትግል ማድረግ ከሁሉም ይጠበቃል፡፡ ዜጎች በተሰማሩበት የስራ መስክና ኃላፊነት የሚያገኙትን የሀገር ሀብትና ንብረት ሊጠብቁት ከዘረፋ ሊከላከሉትም ይገባል፡፡
ሙስና ዘረፋ የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ችግር ግዜ ቢወስዱም ደረጃ በደረጃ በሂደት እየተወገዱ ይሄዳሉ፡፡ ከሀገራችን ምድር ተነቅለው መጥፋት አለባቸው፡፡ ትውልድን ሀገርን የሚበክሉ ተላላፊ በሽታዎች ናቸው፡፡
ሀገራዊ ችግሮቻችን እልፍ ናቸው፡፡ ሁሉንም ለመወጣት የምንችለው በዘረኝነትና በጎጠኝነት በሽታ ሳንጠለፍ ሕብረትና አንድነታችንን አጽንተን መከፋፈልን አስወግደን ከስሜታዊነትና ከጥላቻ ወጥተን ለጋራ ሀገራችን በከፍተኛ ብሔራዊ ፍቅርና ስሜት ጸንተን መቆም ስንችል ብቻ ነው፡፡ ተቆጥረው የተቀመጡት መፈታት ያለባቸው ችግሮቻችን ለኢሕአዴግ የተሰጡ በኢሕአዴግ አቅም ብቻ የሚፈቱ አይደሉም፡፡ ሁላችንም በጋራ ቆመን በመረባረብ ልንፈታቸው ይገባል፡፡

መሐመድ አማን

Published in አጀንዳ

ፈጣን የኢኮኖሚ ልማት፣የዴሞክራሲ ግንባታና ሰላምን ማረጋገጥ ለአገራችን የህልውና ጉዳይ መሆኑ በውጭ ጉዳይና አገራዊ ደህንነት ፖሊሲያችን ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ በዚህም መሰረት መንግሥት ለህልውናችን ቁልፍ ለሆኑ ጉዳዮች ከምንም በላይ ቅድሚያ በመስጠት እየሰራ ይገኛል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ኃላፊነታቸውን ከተረከቡ ማግስት ጀምሮ ቅድሚያ የሰጧቸው ዋና ዋና ጉዳዮች እነዚህን መሰረታዊ ጉዳዮች ታሳቢ ያደረጉ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን በተረከቡ ማግስት ቅድሚያ የሰጡት ለሰላም ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም መሰረት በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች በመገኘት ከህዝቡ ጋር ሰፋ ያለ ምክክርና ውይይት አድርገዋል፡፡
እነዚህ የውይይት መድረኮች በአገራችን ካለፉት ሁለት አመታት ወዲህ የተከሰቱትን የሰላም መደፍረስ ችግሮች ለመፍታትና ህዝቡን ወደ አንድነት በማምጣት በቀጣይ ለተያዘው የልማት እቅድ በጋራ ለማሰለፍ የላቀ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል፡፡ በውይይቶቹም ወቅት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተገኙት አስተያየቶች ይህንኑ የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን ደግሞ ትኩረታቸውን ወደ ጎረቤት አገራት በማድረግ የጀመሩትን ስራ እያሰፉ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ አንፃር በጅቡቲና ሱዳን ያደረጉት ጉብኝት ማሳያ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የውጭ ጉዳይና የአገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂያችን ብሔራዊ ጥቅማችንን የማስጠበቅና አገራዊ ህልውናችንን የማረጋገጥ ተልዕኮ ያለው ሆኖ የተቀረፀ ነው፡፡
በዚህም መሰረት አካሄዳችንን ከውስጥ ወደ ውጭ በማድረግ የራሳችንን የቤት ስራ በቅድሚያ እንድንሰራና ውስጣዊ ጉድለቶችን ከለየን በኋላ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂው እነዚህን ክፍተቶች ለማሟላት እንዲያስችል ሆኖ ተቀርጿል፡፡ መንግስት በዚህ ፖሊሲ ላይ በግልፅ እንዳስቀመጠው ሃገራችን የጀመረችውን ልማት ከግብ ልታደርስ የምትችለው የአካባቢ ሁኔታ ለልማቱ የተመቸ ሲሆን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በቅድሚያ እኛው ራሳችን የራሳችንን የቤት ስራ በውስጥ ካጠናቀቅን በኋላ የሚጎድሉንን ለይተን ማስቀመጥና በዚያ ላይ መረባረብ ተገቢ መሆኑን በግልፅ አስቀምጧል፡፡
ከዚህ አንጻር በተለይ ከአፍሪካ ቀንድ አገራት ጋር የሚኖረን ግንኙነት በአንድ በኩል ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን መሰረት ያደረገ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የጋራ ሰላምና ደህንነትን ከማረጋገጥ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከጎረቤቶቻችን ጋር ያለውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጉዳይ ስንመለከት በቅድሚያ የወደብ ጉዳይ ሊነሳ ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀንድ አገራት ወደብ የሌላት አገር ብትሆንም በሌላ በኩል ደግሞ ኢኮኖሚዋ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ይህ የኢትዮጵያ እድገት በነዚህ አገራት ወደቦች ይበልጥ ተጠቃሚ እንድንሆን ከማድረጉም በላይ ለጎረቤቶቻችንም ከፍተኛ ጠቀሜታን የሚያስገኝ ነው፡፡
ሌላው መሰረታዊ ጉዳይ ደግሞ ከዴሞክራሲያችን ጋር የተያያዘው ጉዳይ ነው፡፡ የጎረቤት አገራት ሰላም መሆን አገራችን ለጀመረችው የሰላምም ሆነ የልማት እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው፡፡ ምክንያቱም የጎረቤት አገራት ሰላም መደፍረስ ለሽብርተኞችና ለአክራሪ ሃይሎች ምቹ ሁኔታን በመክፈት የኢትዮጵያንም ሰላም የሚያውክ በመሆኑ ለጋራ ሰላም በጋራ መስራት ለአካባቢው ሃገራት የጋራ ተጠቃሚነትን ያረጋግጣል፡፡
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ትኩረታቸውን ወደ ውጭ አገራት በማዞር በጅቡቲና ሱዳን ያደረጓቸው ጉብኝቶች ከዚህ የመነጨ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሃገር ውስጥ ከጀመሩት ሰላምን የማረጋገጥ ተግባር ጎን ለጎን አካባቢያዊ ሰላምና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ትኩረት መስጠታቸውም ይህንን የሃገራችንን ፖሊሲ መሰረት በማድረግ የተከናወነ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጅቡቲ ባደረጉት ጉብኝት ሁለቱ አገራት የኢኮኖሚ ውህደትን እውን ለማድረግ ያስቻለና በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያስቻለ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትላንት ጀምሮም በሱዳን ተመሳሳይ ጉብኝት እያደረጉ ይገኛሉ ፡፡ ይህም በሁለቱ አገራት መካከል የቆየውን በወንድማማችነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ለማጠናከርና በጎረቤት አገራት መካከል ያለውን የሰላምና ኢኮኖሚ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር ጠቃሚ እንደሆነም ይታመናል፡፡
በሌላ በኩል ለይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ የሚገኙት የእስራኤሉ ፕሬዚዳንት ሬዩቪን ሪቭሊን በተለይ አገራችን በዲፕሎማሲው መስክ ያላት ተቀባይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የሚያመላክት ነው፡፡ ኢትዮጵያና እስራኤል ከአንድ ሺህ አመት የዘለለ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን ከ1956 ዓ.ም ጀምሮም ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሁለቱ አገሮች በግብርና ዘርፍ ጠንካራ ትስስር ያላቸው ሲሆን በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በትምህርት፣ በደህንነት፣ በጸጥታና ሽብርተኝነትን በመዋጋት ላይም ጠንካራ የጋራ ትብብር አላቸው። የአሁኑ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝትም ይህንን ግንኙነት ለማጠናከር ከማገዙም በላይ ኢትዮጵያ በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ ያላትን ተቀባይነት እንደሚያሳድገው ይታመናል፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አመታት ከነበረችበት የሰላም እጦት ችግር ወጥታ አዲስ የሰላም ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ ምዕራፍ ደግሞ የውስጥም ሆነ የአካባቢ ሰላማችንን የምናረጋግጥበት ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ፊታችንን ወደ ልማት የምናዞርበት የሽግግር ወቅት ነው፡፡ እያንዳንዱ የአገራችን ዜጋም ይህንን የውስጥም ሆነ የአካባቢ በጎ ምላሽ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ወደራሱ ሊወስደውና ሊጠቀምበት ይገባል፡፡ በተለይ የውስጥና የአካባቢ ሰላም ሲኖር ሰርቶ ራስንም ሆነ አገርን ለመወለጥ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር በመሆኑ እድሉን በመጠቀም ሌት ተቀን ሰርተን ራሳችንንም ሆነ አገራችንን ለማሳደግ ልንተጋ ይገባል፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።