Items filtered by date: Friday, 04 May 2018

በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች እንዲሁም ስኬታማ ታሪክ ያላቸው ታላላቅ ክለቦች በታዳጊ እና ወጣት የእግር ኳስ ፕሮጀክቶችና በአካዳሚዎቻቸው መሥራት መቻላቸው ጠንካራና በክህሎታቸው የዳበሩ ተጫዋቾችን ማፍራት አስችሏቸዋል፡፡
ቁጥሩ አናሳ ይሁን እንጂ ታዳጊዎችን ከልጅነታቸው ጀምሮ በእግር ኳሱ ውስጥ የማሰለፍ ልምድ በአፍሪካ የእግር ኳስ አካዳሚዎች እንቅስቃሴ ላይም ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ በተለይ የምዕራብ አፍሪካ አገራት ተጠናክረዋል፡፡ በዚህ የአህጉሪቱ ዞን በሺዎች በሚቆጠሩ አካዳሚዎች በመሥራት ታዳጊዎችን ማፍራት ተሳክቶላቸዋል፡፡ የምዕራብ አፍሪካ አገራት የእግር ኳስ አካዳሚዎች እና ማሰልጠኛዎች አማካኝነት በአውሮፓ እግር ኳስ ተፈላጊ የሆኑ ፕሮፌሽናል ተጫዋቾችን በማፍራት የረጅም ጊዜ ልምድ አላቸው፡፡ እነ ጆርጅ ዊሃ፤ ኑዋንኩ ካኑ፣ ዲዴዬር ድሮግባ፣ ኢማኑዌል አደባዬር፣ ያያ ቱሬ የመሳሰሉ ምርጥ ፕሮፌሽናሎችን በማውጣት በዓለም እግር ኳስ ከፍተኛ ለውጥ መፍጠር ችለዋል፡፡
በተለያዩ የዕድሜ ደረጃዎች የሚደረጉ ውድድሮች አገርን ለሚወክሉ ብሄራዊ ቡድኖችና ዘላቂ ውጤታማነት ያስፈልጋሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በምታደርጋቸው ውድድሮች ለሚታዩት ክፍተቶች ተተኪዎች የሉም ብሎ መንቀፍ የተለመደ በመሆኑ በስፖርት ባለሙያዎች የሚሰጠውን ‹‹በታዳጊዎች ላይ መሥራት›› የሚለውን አስተያየት በመቀበል እንደሌሎች የአፍሪካና የዓለም አገራት አገሪቱ ላይ ፍላጎቱ ያላቸው ታዳጊዎችን ከልጅነታቸው ጀምሮ ለማብቃት እንቅስቃሴዎች በመደረግ ላይ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱት ተግባራት ደግሞ በበጋ መርሐ-ግብር በአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኩል በየዓመቱ በጃንሜዳ የሚካሄደው የታዳጊዎች ሻምፒዮና አንዱ ነው፡፡
የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት አቶ በለጠ ዘውዴ እንደሚሉት፤ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ላለፉት ዓመታት ከ15 እና ከ17 ዓመት በታች የታዳጊ ወጣቶችን ውድድር አካሂዷል፡፡ ባለፉት ዓመታት በውድድሩ የቁጥር ብዛት ልቆ የተገኘ ሲሆን፤ ቁጥሩን ወደ ጥራት ለማምጣት በተደረገው ጥረት ቀጣይነት ያለውን ውጤት ለማስጠበቅ ታዳጊዎች ለክለቦችና ለአገር እንዲሁም ለራሳቸው እንዲጠቅሙ በመታሰቡ ከህፃንነት ጊዜአቸው ጀምሮ መሰረት ይዘው የሚያድጉበትን መንገድ በመለየት እየተሠራ ነው፡፡ ለዚህም ፌዴሬሽኑ በሌሎች ክልሎችም ይሁን በብሄራዊ ቡድን ደረጃ እንኳን ያልታየ ከ15 ዓመት በታች በየዓመቱ የማይቆራረጥ ውድድር ያካሂዳል፡፡ እንደ አዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተሳታፊ የሆኑ ታዳጊ ወጣቶች የዕድሜ ገደብ ከ15 ዓመት በታች ይሁን እንጂ ከ13 ዓመት ጀምሮ የሚጫወቱም ታዳጊዎች አሉ፡፡ ጥሩ የእግር ኳስ ብቃትም አላቸው፡፡ ህፃናት ከዚህ ዕድሜአቸው ጀምረው በስፖርቱ የሚያድጉበትን መንገድ ማመቻቸት ተተኪ ስፖርተኞች ላይ የሚፈጠረውን ክፍተት ይሞላል፡፡ በተለይ ፌዴሬሽኑ ይህን ዓይነት ውድድር ማዘጋጀት ከጀመረ በርከት ያለ ጊዜ ቢያሳልፍም፤ ከሁለት ዓመታት ወዲህ ግን በጥራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው፡፡
ምልመላ
አቶ በለጠ በሰጡት ማብራሪያ፤ በዕድሜአቸው እስከ አራትና ሦስት ዓመት በተመሳሳይ የውድድር ዘርፍ መቆየት የሚችሉ ታዳጊዎች ይመለመላሉ፡፡ በውድድር ዓመቱ ተሳታፊ ከሆኑት ቡድኖች ብዙሃኑ የግል ቡድኖች እንደመሆናቸው፤ በተለይ የዕድሜ ተገቢነትን ለመለየት መልማይ ቡድን በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ተዋቅሯል፡፡ በኮሚቴው ውስጥ የህክምና ባለሙያዎች፣ አሰልጣኞችና ሌሎች ሙያተኞች ተካትተዋል፡፡ በዚህ ደረጃ ያለው ሥራ መልካም የሚባል ነው፡፡ በችሎታቸው ጥሩ የሆኑና በተለያዩ ክለቦች ላይ የመግባት ዕድል ያገኙ ታዳጊዎችን ማፍራት ተችሏል፡፡ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ የሚሳተፉ ታዳጊዎች አብዛኞቹ ከዚህ የፉክክር መድረክ የተገኙ ናቸው፡፡ ይህን ያመጣው ደግሞ ዕድሜ ላይ በትኩረት መሰራቱ ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ የዕድሜ ተገቢነት ቅሬታዎችን ለማስቀረት ትኩረት በማድረጉ አሁን ያለው የውድድር ብዛትም አነስተኛ ነው፡፡ ከ17 ዓመት በታች ያሉት ታዳጊዎች ከዋና ቡድኑ 17 ዓመት በታች ጋር እንዲወዳደሩም ጥያቄ የቀረበበት ወቅት አለ፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ተጫዋቾቹ በዕድሜ ሲመዘኑ ከዋናው ብሄራዊ ቡድን አንፃር ተዓማኒነት የሚታይባቸው በመሆናቸው ነው፡፡
በቴክኒክ ክፍሉ ውስጥ ያሉት የህክምና ባለሙያዎች በተለይ በምልመላው ወቅት ከዕድሜ ጋር ተያይዞ የሚሰሩ ሥራዎች ላይ መሪ ተዋናይ ናቸው፡፡ የልጆች የግል ማህደር በአሰልጣኞች ተሞልቶ እንዲመጣ ከተደረገ በኋላ፤ የመለየቱ ሥራ የሚከናወነው በእይታ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ጊዜ የልጆቹን ዕድሜ ለመለየት በጨዋታ ላይ ከተቃራኒ ቡድን ጋር ያለውን ልዩነት በማየትም ይሆናል፡፡ ለዚህም ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ በመገኘት ምልከታው ይካሄዳል፡፡
የዕድሜ መመርመሪያ መሣሪያ አለመኖር
አቶ በለጠ፤ ‹‹የዕድሜ መመርመሪያ መሣሪያ አለመኖሩ በፌዴሬሽኑ ላይና በተሳታፊ ቡድኖች ትልቅ ጉዳት እያመጣ ነው፡፡ አብዛኞቹ የታዳጊ ቡድኖች ተሳታፊዎች የግል ቡድኖች እንደመሆናቸው መጠን መወዳደር ቢፈልጉም በዕድሜ ምክንያት ተጫዋቾች ሲወድቁባቸው ከውድድር ይወጣሉ፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ የዕድሜ መለያው አሰራር ኋላ ቀር በመሆኑ ነው፡፡ ክለቦቹ ዕድሜ ሲያስመረምሩ በሚመለከቱት ሰዎች ላይ ዕምነት የማጣት ሁኔታዎችም ይፈጠራሉ፡፡ ፍትሃዊነቱ ላይም ብዙ ጊዜ ቅሬታዎች ይነሳሉ፡፡›› ይላሉ፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤ የዕድሜ መመርመሪያ ወደ አገር ቤት አስመጥቶ ለመጠቀም ከባድ ነው፡፡ ብዙ ጊዜም ይወስዳል፡፡ ይህንን መሥራት ያለበት ግን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ነው፡፡ ምክንያቱም ይህንን የማድረግ አቅም ከክልል ፌዴሬሽኖች በላይ ነውና፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከፊፋ ጋር በሚያደርገው መልካም ግንኙነት ይህንን ጉዳይ እንደ አብይ አጀንዳ ቢያደርገው መሣሪያውን የማግኘት ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ በመሆኑም መሣሪያው አገር ቤት እንዲኖር አድርጎ ለራሱም ለክልሎችም ማሰራጨት የሚችልበት ሁኔታ ቢፈጠር በዕድሜ ረገድ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ይቻላል፡፡ በመሣሪያ አቅርቦቱ በአገሪቱ ላይ ያሉና የእግር ኳስ ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊዎችን በመለየት በየዕድሜ ክልላቸው እንዲጫወቱና ለብሄራዊ ቡድን እንዲበቁ ማድረግ ይቻላል፡፡ በየዓመቱ ለህክምና የሚወጣውን ወጪም ይቀንሳል፡፡ ጥራት ያለው እግር ኳስም መመልከትም ይቻላል፡፡
የክልሎች አቅም መሣሪያውን ወደ አገር ቤት ማስመጣት ሳይሆን ሙያተኞችን መቅጠር ነው፡፡ በዓይን በማየት ብቻ የሚካሄድ ምርመራም ፍትሃዊ አይደለም፡፡ በየዓመቱ የታዳጊዎችን ዕድሜ ለመለየት በልምድና በእይታ ብቻ እያከናወኑ መሄዱ ይሰለቻል፡፡ መሣሪያው አለመኖሩ በራሱ የፌዴሬሽኑ ትልቅ ፈተና ከመሆን ባሻገር ተመጣጣኝ የሆነ ፉክክር እንዳይኖርና ስፖርታዊ ጨዋነት እንዲጓደል የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡
አንዳንድ ጊዜ በእይታ ብቻ ዕድሜው ትንሽ የሆነ ተጨዋች እንዳይሳተፍ የሚደርግበት ሁኔታ ይከሰታል፡፡ ታዳጊው ብዙ ነገር ሜዳ ላይ ሊሰራ እንደሚችል እየታወቀ በልምድ በሚሰራ አካሄድ ተስፋው ይቀጭጫል፡፡ ይህ በራሱ በአገሪቷ እግር ኳስ እድገት ውስጥ ሊያበረክት የሚገባውን በጎ ሚና ያሳጠዋል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የመሣሪያው ጉዳይ የብሄራዊ ፌዴሬሽኑን ትልቅ እገዛ የሚፈልግ ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ ከውድድር ባለፈ ቴክኒካዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እጁን ማስገባት ይኖርበታል፡፡ የታዳጊዎች መነሻቸው የክልልና ከተማ አስተዳደሮች ውስጥ በሚገኙ ፌዴሬሽኖች እንደመሆናቸው የዕድሜ ተገቢነት ችግሮችን ለመፍታት ተዋዕረዳዊ ሥራ መሰራት አለበት፡፡ የመመርመሪያ መሣሪያ ቢኖር ኖሮ የተሳታፊ ክለቦች ቁጥር ስለሚበዛ ታዳጊ ወጣቶችን በጥራትና በብዛት ማፍራት ይቻል ነበር፡፡ በአሰልጣኞችና በፌዴሬሽኑ መካከል መተማመን ይኖር ነበር፡፡ በዕድሜ ገደብ ምክንያት የሚፈጠሩ አሉባልታዎችና ጭቅጭቆች ይቀሩ ነበር፡፡ የተጨዋቾች መረጃም በአግባቡ መደራጀት ይችላል፡፡ የአዲስ አበባ እግር ኳሽ ፌዴሬሽን ጉዳዩ ከአቅም በላይ መሆኑን ቢያምንም ሙከራዎች ግን ይቀጥላሉ፡፡ ለአብነትም በቅርቡ በዕድሜ ተገቢነት ምክንያት ቅጣት የተጣለበት የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ታዳጊ ቡድን መሣሪያው በአገር ቤት ገብቶ ከስሩ መሥራት ቢቻል ኖሮ ለእንዲህ አይነት ስህተት ከመዳረግ ማምለጥ ይቻል ነበር፡፡
የክልልና ከተማ አስተዳደር ፌዴሬሽኖች የሚሰሩት ለግላቸው ሳይሆን በአገሪቱ ወጥነት ያለው የእግር ኳስ ችሎታ እንዲኖር ስለሆነ ዋናው ፌዴሬሽን አቅሙን አጎልብቶ ይህንን ችግር መቅረፍ ይኖርበታል፡፡
የውድድር መርሐ ግብር
‹‹በሥራ ቀናት በፍፁም ጨዋታ አይኖርም፡፡ ቅዳሜና እሁድ የበዓላት ቀን እንዲሁም ከትምህርትና ሥራ ሰዓት ውጭ ውድድሮች ይካሄዳሉ፡፡ ውድድሩ የሚካሄደው የታዳጊ ወጣቶቹ ቤተሰቦችን ጓደኞቻቸው በተገኙበትና ለማየት አመቺ በሆኑ የዕረፍት ቀናት ላይ ነው፡፡ ይህም ታዳጊዎቹ ከትምህርታቸው እንዳይስተጓጎሉና ሁለቱንም ጎን ለጎን እንዲያስኬዱት ታሳቢ ተደርጎ ነው፡፡ የመወዳደሪያ ጊዜው ልጆች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይርቁ አድርጓል፡፡ ብዙ ኪሎ ሜትር ሄደው መወዳደር እንደሌለባቸው በማመን ማዕከላዊ በሆነው የውድድር ስፍራ እንዲሳተፉም ተደርጓል፡፡›› በማለት የታዳጊ ወጣቶቹ የውድድር መረሐ ግብር የጊዜና የቦታ አመቺነት መኖሩን አቶ በለጠ ይገልፃሉ፡፡
2010 ዓ.ም
በዘንድሮው የበጋ የታዳጊዎች ውድድር በእግር ኳስ ክህሎት ለኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ መሆን የሚችሉ ታዳጊዎች መታየት መቻላቸውን የሚናገሩት አቶ በለጠ፤ በውድድር ጥራትም ሆነ በተጨዋቾች ክህሎት የ2010 ዓ.ም የተሻለ የውድድር ዘመን እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ የተወዳዳሪ ክለቦች ቁጥር ማነሱ እያንዳንዱን ክለብ እንቅስቃሴና የተጨዋቾችን ብቃት ነጥሎ ለማየት እንደተቻለ፣ በተጋጣሚ ቡድኖች መካከል ያለው ፉክክርም አስደማሚ እንደነበር፣ የኢትዮጵያ መላ ጨዋታ ላይ የመሳተፍ አቅም ያላቸው ተጨዋቾች ብቅ ማለት መቻላቸው፣ በዕድሜ ረገድም ሁሉም ክለብ ተመሳሳይና ተመጣጣኝ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ መሆናቸው፣ ደረጃ ውስጥ ያሉ ቡድኖችም ነጥባቸው ብዙ ያልተራራቀና አሸናፊው ማን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት ጉጉት የሚፈጥር እንደነበርና፤ ይህም ተፎካካሪ ክለቦች ተመጣጣኝ ችሎታና አቅም እንዳላቸው ማሳያ መሆኑን አቶ በለጠ ተናግረዋል፡፡ የውድድር መርሐ ግብሩም በተያዘለት ጊዜ እየተጠናቀቀ መሆኑንም አክለዋል፡፡
የተወዳዳሪ ክለቦች ቁጥር ማነስ ለምን?
የጃንሜዳው የበጋ የታዳጊዎች ውድድር ከባለፉት የተሳትፎ ዘመኖች በ2010 ዓ.ም ከሌሎቹ ዓመታት በተለየ መልኩ የተሳታፊ ቡድኖች ቁጥር ቀንሷል፡፡ አቶ በለጠ ይህንኑ አስመልክተው እንደተናገሩት፤ አንዳንድ አሰልጣኞች ከጨዋታው ይልቅ ውጤት ፍለጋ ላይ በማተኮር ዕድሜአቸው ከፍ ያሉ ተወዳዳሪዎችን ያስመዘግባሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በቴክኒክ ኮሚቴውና በህክምና ቡድን የልጆቹ ዕድሜ ተጣርቶ እንዲወድቁ ሲደረግ ከውድድር የሚርቁበት አጋጣሚ ስላለ ቁጥሩ ሊያንስ ችሏል፡፡ አዲስ አበባ ላይ የሚወዳደሩ ክለቦች አብዛኞቹ የግል ተወዳዳሪዎች ስለሆኑ መወዳደሪያ ገንዘብ፣ ትጥቅና ሌሎች ግብአቶችን አሟልተው ወደ ፉክክር የሚገቡት ከራሳቸው በመሆኑ የሚደገፉበት መንገድ የለም፡፡ ስለዚህም ድጋፉን ካጡ አይመዘገቡም፡፡
ከዚህ ሌላ ታዳጊዎችን ለረጅም ዓመታት ያሰለጠኑ አሰልጣኞች ተስፋ የማጣት ነገር ይታይባቸዋል፡፡ በተለይ ለረጅም ጊዜ ያሰለጠኗቸውን ወጣቶች በጥሩ አቋም ላይ ሲሆኑ ሌላ ክለብ ይወስድባቸዋል፡፡ ይህ አሰልጣኞችን የሚጠቅም ነገር የለውም፡፡ ተጨዋቾች ከአማተርነት ወደ ሌላ ቡድን ሲዟዟሩ ያለ ምንም ጥቅማ ጥቅም ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ አሰልጣኞችን ሊጠቅም የሚችል ነገር ባለመኖሩ አብዛኞቹ ‹‹ለምን እንደክማለን›› በሚል ስሜት እራሳቸውን ከአሰልጣኝነት ያገልላሉ፡፡ የአሰልጣኝ ተስፋ እጥረትም የውድድር ቁጥሩን ዝቅ እንዲል አድርጓል፡፡
በዚህ ዙሪያ ወደ ፊት ፌዴሬሽኑ የውድድር ስያሜዎችን በመሸጥና አጋር ሊሆኑ የሚችሉ ድርጅቶችን እንዲሁም ባለ ሀብቶችን በማካተት ክለቦች የሚደገፉበትን መንገድ ሊያመቻች እንደሚገባው ሥራ አስፈፃሚው በተደጋጋሚ ተነጋግሯል፡፡ ነገር ግⶰን በዚህ ረገድ ወደ ተግባር አልተገባም፡፡ ይህም የፌዴሬሽኑ ክፍተት ነው፡፡
የተጨዋቾችን ዝውውር በተመለከተ ግን አሰልጣኞችም ሆኑ የሚያሰለጥኑት ክለብ ተጠቃሚ ይሆን ዘንድም ወደ ፊት ደንቦች ሊዘጋጁ ይገባል፡፡ ፌዴሬሽኑም ድጋፍ ለማድረግ አዳዲስ አሰራሮችን ያመጣል፡፡ የክለቦች ትስስርም ይፈጠራል፡፡ የመመዝገቢያ ክፍያውም ከአቅም በላይ ከሆነ በቀጣይ የውድድር መርሃ ግብሮች ስራ አስፈፃሚው ተወያይቶ የሚስተካከልበትን መንገድ ያመቻቻል፡፡ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመነጋገር ደረጃ ውስጥ የሚገቡ ክለቦች ተመሳሳይ ዕድሜ ውስጥ ካሉ የዋናው ቡድን ተጨዋቾችና ክለቦች ጋር የሚለዩ በትን ሁኔታዎች በማመቻቸት ለአገር የሚመጥኑ ተጨዋቾች የሚታዩበትን አሰራር ለመዘርጋት ታሳቢ ተደርጓል፡፡ ይህ ብዙ ክለቦች ወደ ውድድር እንዲመጡ ያስችላል፡፡ ተጨዋቾች ልምድ ባላቸው ብዙ አሰልጣኞች መታየታቸውን ሲያውቁ ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ፡፡ የክልል ክለቦችም ይነቃቃሉ፡፡
ተሞክሮ
አቶ በለጠ፤ ‹‹ፌዴሬሽኑ በአቅም ውስንነት ምክንያት ወደ ሌሎች ክልሎች በማቅናት የወሰደው ተሞክሮ የለም፡፡ በዋናው ፌዴሬሽን በኩል በሚካሄዱ መድረኮች ላይ ተገኝቶ ለመከታተል አመቺ ሁኔታዎች የሉም፡፡ በዚህ ረገድ ግን የልምድ ለውውጥ በከፍተኛ ሁኔታ መኖር እንዳለበት ፌዴሬሽኑ ያምናል፡፡ ተሞክሮ የምንወስድበት መንገድ የግድ ያስፈልጋል፡፡ ተሞክሮ ቀስሞ የመሥራት ባህል መኖሩ ዞሮ ዞሮ የሚጠቅመው የአገሪቷን ስፖርት ነው፡፡ የትኛው ክልል ላይ ነው የተሻለ እንቅስቃሴ ያለው የሚለውን መርምሮ መያዝ ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚያወዳድራቸው ክለቦች ሌሎች ክልሎች ላይ ሄደው ልምድ ባይወስዱም የተወሰኑ ክልሎች ግን ወደ ፌዴሬሽኑ መጥተው ልምድ ወስደዋል፡፡ ፌዴሬሽኑ ልምድ ለመወስድ ብዙም ርቀት አለመጓዙ ግን እንደ ክፍተት የሚታይ ነው፡፡ ወደ ፊት ከአቻ ፌዴሬሽኖች ጋር የሚደረገውን ልምድ የመቅሰም ሂደት ይኖራል፡፡›› ብለዋል፡፡
ድጋፍ
እንደ አቶ በለጠ ማብራሪያ፤ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቢያንስ ለአንድ ክለብ ከ20 እስከ 30ሺ ብር ወጪ ያደርጋል፡፡ ለዳኞች፣ ለኮሚሽነሮች፣ ለሜዳ ጉዳዮችም ወጪ ያወጣል፣ በተለይ በክረምት መርሃ ግብር ተደርጎ ከነበረው የሲቲ ካፕ ውድድር የተገኘው ገንዘብ ለክለቦች ከተከፋፈለ በኋላ ቀሪው ታዳጊ ወጣቶችን ጨምሮ በፌዴሬሽኑ ውስጥ ሆነው ለሚወዳደሩ ቡድኖች ፈሰስ ይደረጋል፡፡ ድጎማው ስለተደረገ ነው የክለቦቹ ክፍያም ቅናሽ የተደረገው፡፡ ለመወዳደር የተመዘገበው ክለብ ግማሽ ፐርሰንቱ ከተገኘው የሲቲ ካፕ ላይ ወጪ ተደርጎለታል፡፡ ድጋፍ ባይደረግ ኖሮ አንድ የታዳጊ ቡድን ለመመዝገብ ብቻ 16ሺ ብር ይፈጅበታል፡፡ ነገር ግን በፌዴሬሽኑ ድጋፍ ስምንት ሺ ብር ከፍለው እንዲሳተፉ እየተደረገ ነው፡፡
ከዚህ ሌላ ከተለያየ አካላት የሚገኙ የስፖርት ትጥቆች አቅም ለሌላቸውና በፕሮጀክት ለታቀፉ ክለቦች በመስጠት ድጋፍ እየተደረገ ነው፡፡
መልዕክት
አሰልጣኞች ከውጤት በላይ ተተኪ ወጣቶችን ማፍራት ላይ ማተኮር ይገባቸዋል፡፡ የሚሉት አቶ በለጠ፤ ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር ተያይዞ በተለይ አሰልጣኞችና የቡድን መሪዎች ለታዳጊ ወጣቶች ሊያሳዩት ሚገባው ነገር በጎ መሆን አለበት፡፡ አሰልጣኞች እንደ መምህራን ስለሚታዩ ተገቢ ያልሆኑና ከስፖርታዊ ጨዋነት የራቁ ድርጊቶችን ማራቅ ይገባቸዋል፡፡ ከልጆቹ ይልቅ ራስን ማስቀደም እየታየ ስለሆነ መስተካከል ይገበዋል፡፡ ድርጊቱ ስር እየሰደደ ከሄደ ሰሞኑን በአገረቷ ትልልቅ የውድድር መድረኮች ላይ የሚስተዋለው ችግር በታዳጊዎችም እየተንጸባረቀ ይሄዳል፡፡ ስፖርታዊ ጨዋነትን ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› ሊባል ይገባል በማለት ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

አዲሱ ገረመው

 

ፌዴሬሽኑ እና ማህበሩ ሊደራደሩ ነው

 

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ዳኞችና ታዛቢዎች ሙያ ማህበር በስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ምክንያት የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጦ ለሦስት ሳምንት ያስተላለፈውን ያለመዳኘት ውሣኔ እንዲያጤን ክለቦችና ፌዴሬሽኑ ጠየቁ፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሰሞኑን በእግር ኳሱ ያጋጠመውን የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል በተመለከተ ትናንት በጁፒተር ሆቴል ለግማሽ ቀን ከሁሉም የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች ጋር መክሯል፡፡ በምክክሩ ላይ የተሳተፉት ክለቦችም የዳኞች ማህበሩ ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች በፍጥነት ምላሽ አግኝተው የተቋረጠው የውድድር መርሐ ግብር እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
በምክክሩ ወቅት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ስቴዲየሞች የሚስተዋለው ሥርዓት አልበኝነት እንደሚያሳስባቸው ያስታወቁት ክለቦቹ፤ የሚወገዝ ተግባር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ዳኞች ካለባቸው ሥጋት አኳያ በማህበራቸው በኩል የወሰዱት እርምጃ ተገቢ ቢሆንም የጨዋታዎች መቋረጥ ግን በርካታ ጥቅሞችን በማሳጣት ለኪሳራ እንደሚዳርጋቸው ገልፀዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ ተጫዋቾች ደመወዝ፣ የካምፕ ውስጥ የምግብና ሌሎች ወጪዎች፣ የስቴዲዮም ገቢ እንዲሁም የተጨዋቾች ኮንትራት ጉዳይ ከሥጋቶቻቸው ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ዳኞችና ታዛቢዎች ሙያ ማህበር ሊቀመንበር ኢንተርናሽናል ዳኛ ትግል ግዛው፤ ክለቦች ከሚያወጡት ከፍተኛ ወጪ አንፃር የተነሱት ጥያቄዎች ተገቢ መሆኑን አምነዋል፡፡ ነገር ግን ማህበሩ ከትናንት በስትያ ባካሄደው ጉባዔ ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች በፌዴሬሽኑ ምላሽ እስካልተሰጠባቸው ድረስ ውሣኔውን እንደሚያከብር ጠቁሟል፡፡ ‹‹አሁኑኑ ለክለቦች ምላሽ ስጡ›› በሚል ከፌዴሬሽኑ ለቀረበላቸው ጥያቄ ግን ‹‹በማህበር ያወጣነውን አቋም በግሌ መሻር አልችልም›› ነገር ግን በራቸው ለድርድር ክፍት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲ ባሻ በበኩላቸው፤ ዳኞቹ ያቀረቡት ጥያቄ መብታቸው እንደሆነ ጠቅሰው ነገር ግን አድማው መፍትሄ እንደማይሆን ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም ፌዴሬሽኑ በማህበሩ በኩል ያቀረቡትን ቅድመ ሁኔታዎች እየተመለከተ ሲሆን መመለስ የሚችሉትን በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጣቸው ለመደራደር እንደሚፈልግ አረጋግጠዋል፡፡ በዚህ መሰረት ሰሞኑን በጋራ ተወያይተው ውድድሩ በፍጥነት እንዲቀጥል ለማህበሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሚያዝያ 22 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስቴዲየም መከላከያ የእግር ኳስ ክለብ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የእግር ኳስ ክለብ ጋር በተደረገው የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ቡድን መሪ በዕለቱ የመሃል ዳኛው ላይ ያደረሰውን ድብደባ ተከትሎ የስፖርት ቤተሰቡ መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ጉዳዩንም በተመለከተ በርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሳይቀር ሽፋን የሰጡት ሲሆን ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጥቃት ያደረሰውን ቡድን መሪ ከሥራ ማሰናበቱ ይታወሳል፡፡

ብሩክ በርሄ

Published in ስፖርት

ለዓድዋ ጦርነት መነሻ ምክንያት የነበረው የውጫሌ ውል የተፈረመው ከ129 ዓመታት በፊት፣ በዚህ ሳምንት (ሚያዚያ 25 ቀን 1881 ዓ.ም) ነበር፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ኢጣሊያ በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ የቅኝ ግዛት ይዞታ ለመመስረት የአካባቢውን ገዢዎች በኃይልም በስምምነትም ለማሳመን ደፋ ቀና ማለቱን ተያያዘችው፡፡ አገሪቱ የቅኝ ግዛት ፍላጎቷን ለማሳካት ለረጅም ጊዜ ስታልማት ወደኖረችው ኢትዮጵያ ድንበር ብቅ ያለችው ገና በጠዋቱ ነበር፡፡ ንጉሰ ነገስት አጤ ዮሐንስ ፬ኛ መተማ ላይ ከደርቡሾች ጋር በሚዋጉበት አጋጣሚና ሕይወታቸው ማለፉ በተሰማ ጊዜ የተፈጠሩት ክስተቶች ጣሊያኖች የኤርትራን አብዛኛውን ክፍል እንዲቆጣጠሩ አስቻሏቸው፡፡
የውጫሌ ውል በ20 አንቀፆች የተከፈለ ሲሆን፤ የተፈረመውም ወሎ ውጫሌ፣ አምባሰል ውስጥ ‹‹ይስማ ንጉሥ›› በተባለ ቦታ ነው፡፡ ከንጉሰ ነገሥት አጤ ዮሐንስ የአገዛዝ ዘመን በኋላ ንግሥናቸው እንደ ሚገባቸው ያመኑት ንጉሥ ምኒልክ (በኋላ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ) ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት ‹‹ወሎ›› ውስጥ ነበሩ፡፡ ስምምነቱ ቶሎ እንዲያልቅላቸው የፈለጉት ጣሊያኖችም ኮንት ፒዬትሮ አንቶኔሊን ወደ ‹‹ወሎ›› ልከው ስምምነቱን ከንጉሥ ምኒልክ ጋር እንዲፈራረም አደረጉ፡፡ ስምምነቱ ሲፈረም አስተርጓሚ ሆነው ያገለገሉት ግራዝማች ዮሴፍ ንጉሤ ነበሩ፡፡
ኮንት ፒዬትሮ አንቶኔሊ ከሮማ የተላከ ለትን የውል ረቂቅ በግራዝማች ዮሴፍ ንጉሤ አስተርጉሞ ንጉሱን በችኮላ አስፈረማቸው፡፡ ይሁን እንጂ በአንቶኔሊ ሴራ የተካተተው የውሉ 17ኛው አንቀጽ በአማርኛና በጣሊያንኛ ቋንቋዎች የትርጉም አለመጣጣም በማስከተሉ ፣ ኃይል የችግሩ መፍቻ እንዲሆን ግድ ሆነ፡፡ ኢትዮጵያና ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ ታላቅ ጦርነት አድርገው ድሉ የኢትዮጵያ ሆነና መላው ዓለም ተገረመ፡፡ ‹‹ይስማ ንጉሥ›› እና ‹‹ዓድዋ››ም የማይነጣጠሉ የታሪክ አሻራዎችን የያዙ ታሪካዊ ስፍራዎች ሆኑ፡፡

አንተነህ ቸሬ 

Published in መዝናኛ

ጣሊያን ከአድዋ ሽንፈት 40 ዓመታት በኋላ በዘመናዊ የጦር መሣሪያና በወታደራዊ ኃይል ይበልጥ ተደራጅታ ኢትዮጵያን በተለያዩ አቅጣጫዎች ወረረች፡፡ ከአድዋው ዘመቻ ያልተሻለ የጦር ትጥቅ የነበራት ኢትዮጵያም የጣሊያንን ጦር በፅናት ተዋጋች፡፡
ምንም እንኳን የጠላት ጦር ሃያል ቢሆንም፤ አርበኞች ግን ከቀን ወደ ቀን ድል እየተቀዳጁ የጣሊያን ወታደሮችን መፈናፈኛና መግቢያ መውጫ አሳጧቸው፡፡ ከጣሊያን ወታደሮች ይማርኳቸው በነበሩ መሣሪያዎች ራሳቸውን እያደራጁ አብዛኛውን የገጠር ክፍል ተቆጣጠሩ፡፡
ከብዙ ትግል በኋላ የኢትዮጵያ አርበኞች በጣሊያን ወታደሮች ላይ ጥቃታቸውን አፋፋሙ፡፡_ጣሊያኖች ክፉኛ ተሸነፉ፡፡ በየቦታው ድል የመሆናቸው ዜና ተነገረ፤_በዘመቻውም ጣሊያኖች አዲስ አበባን ለቅቀው ፈረጠጡ፡፡ ንጉሰ ነገስቱም ሚያዝያ 27 በአዲስ አበባ ታላቁ ቤተ-መንግሥት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አውለበለቡ፡፡ በአርበኞች ታላቅ ተጋድሎ፤ ኢትዮጵያ በዓለም ፊት በልጆቿ መስዋዕትነትና የደም ማኅተም ነፃነቷን አፀናች፡፡
አካኪ_ዘራፍ_አካኪ_ዘራፍ፤

ጭው_ሲል_ገዳይ_ደጀን_ሲላላ፣
የጠቅል_አሽከር_የጠቅል_ባላ።

ጎራዴ_መዞ_ሲሄድ_ከቤቱ፣
ወየው_ሰው_ፈጀ_አለች_እናቱ፡፡

እንኳን_እናቱ_የወለደችው፤
ኮራች_አማቱ_የተጋባችው፡፡

በሰፊ_አውድማ_የተበጠረው፤
ገለባው_ሄዶ_ምርቱ_የቀረው፡፡
ዘራፍ_ሰው_በሰው፣
በደረሰበት_ባፎቄ_እሚያርሰው።

ሰንደቅ_አላማ_ኮከብ_ሲመስል፣
ነጋሪት_አብጅር_አብጅር_ሲል፣
መትረየስ_ሲጮህ_መድፉ_ሲያጓራ፣
ደጀን_ሲበተን_እርሳስ_ሲዘራ፣
አጣድፎ_ገዳይ_በያዘው_ጣምራ፤
ባባቱ_ወጥቷል_ልጁም_አይፈራ፤
አንድ_ለናቱ_የሜዳ_ጎራ፡፡ ......
እንዲህ ባለ ፉከራ ነበር አገርን ለማስከበር ሲሉ ጀግኖች አርበኞች በጦር ግንባር ላይ ያለ ፍርሃትና ስጋት ጠላታቸውን በጎራዴ ያጠቁት፡፡ ደፋርነትና ቆራጥነት በልበ ሙሉ የወኔ ጀግንነት በኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ቀርጸው ለራሳቸው ሳይኖሩ ስለኛ ኖረው ለአገራችን ክብር አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍስሰው ኢትዮጵያን ያቆዩልን፡፡
እኛስ የዚህ ዘመን ትውልድ አባል የሆነው የአገር አሻራችን በምን ይታወስ? እንደ ቀድሞዎቹ አገርን ከወራሪ ጦር በመከላከል ? ወይስ አፈሙዙን የሰበቀብንን ድህነትን በመዋጋት? ወይስ የባህር ማዶ ፋሽን ተከታይ ወይስ እጅና እግራችንን አጣጥፈን በመቀመጥ የአገርና የቤተሰብ ሸክም በመሆን? ንገሩኝ እስኪ የኛስ የድል ብስራት ምን ይሁን?
እኔ አርበኝነትን የማየው ከራስ ጉዳይ በላይ ለሆነ ትልቅ አላማ ራስን እንደማጨት ነው፡፡ እንግዲህ የእኛ ትውልድ በዚህ ሚዛን ላይ ቢወጣ ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ በውስጡ አገርን የሚያክል ነገር ይዞ ነው ያለው፡፡ ነገር ግን ጀግና መሆን ይህንን እውነት ከፍታው ላይ ቆሞ ማሰብን ይጠይቃል፡፡ የእኛ ትውልድ ከራሱ በላይ ቤተሰቡንም እንኳ በወጉ የሚመክት አይደለም፡፡ በብዙ መጠን ከሽፏል፡፡ ጀግና አለመሆን አንድ ነገር ነው፡፡ ይሄ ትውልድ ግን ማንነቱን ከመሳቱም በላይ በነውር የሚያጌጥ ነው፡፡ ቀበቶህን ከፍ አድርግ፣ ሱሪህን በወጉ ታጠቅ፣...የሚለውን እንደነፃነቱ ጠላት የሚቆጥር ትውልድ ተፈጥሯል፡፡ እንግዲህ የጀግኖቹ የነፃነት ትርጉምና የእኛው የነፃነት ትርጉም ለየቅል ነው፡፡
በአባቶቻችን የተገኘው የነፃነት ትርጓሜ ከአገርም በላይ አህጉራዊ ነበር፡፡ ነውም፡፡ አንዳንዴ የእውነት የእነርሱ ልጆች መሆናችንን እጠራጠራለሁ፡፡ በአሁኑ ወቅት እኮ ቅኝ ግዛት ባለመገዛታችን የሚቆጨው ወጣት ቁጥሩ ጥቂት አይባልም፡፡ ይህ ሁሉ እንግዲህ መነሻው እምነት ነው፡፡ ስለነፃነት ያለን እምነት፡፡ ከሁሉም በላይ አሳፋሪው ነገር ታሪኮቻችንን በቅርጫ ለመከፋፈል የምንጥረው ነው፣ የተቀላቀለውን ደማችንን ቆፍረን ለየብቻችን ለመጥለፍ እንታትራለን! ያም ሆነ ይህ ጀግንነት አሻግሮ ማየትን ይጠይቃል፡፡ እየሞቱ ህያው መሆንን፣ ከጊዜ በላይ መሆንን፣ ከራስም በላይ ማሰብን ይጠይቃል፡፡ ትልቁን ለማሰብ ደግሞ ከፍታው ላይ መውጣት ያሻል፡፡ ለዚያም ሳይሆን አይቀርም ተራሮቻችን የጀግኖቻችን መገለጫ ሆነው ለዘላለሙ የተፃፉት!
ስነ ምግባርም ተባለ ማንኛውም እሴት ምንጩ ለራስ የሚሰጥ ግምት ነው፡፡ ራሱን የማያከብር ማንንም ሊያከብር አይችልም፡፡ በግልፅ ቋንቋ ታሪካችንን ጨምሮ ሌሎች እሴቶቻችንን የምንንቅ ይመስለናል እንጂ የናቅነው ራሳችንን ነው፡፡ ስለዚህ አገሩን የሚወድ ትውልድ መፍጠር ከተፈለገ ከሁሉ በፊት ራሱን የሚያከብር ዜጋ መፍጠር ይገባል፡፡ እኛ ማሳለጫ ውስጥ ተደብቀን የኔብጤውን ከጎኑ ከሚያልፈው ቅንጡ መኪና ጋ ፎቶ በማንሳት መነጋገሪያ ማድረግ ጀግንነት እንዳልሆነ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡
በድሮው ዘመን ቀረርቶ የሚሰማና ድንፋታ የሚያይ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ልቡ ሙሉ ይሆናል፡፡ ባላጋራውን ከፊቱ ሲያይ ጸጉሩ ይቆማል ደሙም ይፈላል፡፡ በተለይ በአገር ከመጡበት ያንቀጠቅጠዋል፡፡ የሚፎክረው ሰው ሲቅበጠበጥና ቁጭ ብድግ ሲል ለተመልካች የራበው አንበሳ ይመስላል፡፡ ፉከራው ለጀግኖች ሃይልን ይሰጣል፤ ለፈሪዎች ህሊናን እንዲገዙ ያደርጋል፡፡ በጊዜው የነበሩ ወጣቶች ይህንን ባዩና በሰሙ ጊዜ አባቶቻቸውን ለማከል እንዲያውም ለመብለጥ ይጥሩ ነበር፡፡ ደረታቸውንም አሳልፈው ለጥይት ይሰጡ ነበር፡፡
እኛ ግን ደረታችን ለጥይት ይቅርና ለጸሀይ መስጠት እንኳን ያሳሳናል፡፡ እየቀላንና እያበጥን በምቾት እየኖርን ወላጆቻችን አጠገባችን ሲቆሙ ስሙኒ እንደሚያክሉ ይሰማናል፡፡ በዚህም የጀግኖቹ የሙት መንፈስ የሚወቅሰን ይመስለኛል፡፡
‹‹ሚስቱን ገድሎ ወደ አማቱ ሸሸ›› የሚል ድንቅ አባባል አለ፡፡ የምንሸሸው ነገር እንዳለ ያስታውቃል፡፡ አስደንጋጩ ነገር የምንሸሸው ከራሳችን መሆኑ ነው፡፡ ተምረን መመረቃችንን እንወደዋለን፡፡ ነገርግን ሙአለ ህፃናት ሆነን በእርሳስ መፃፍ አልነበረብንም እንላለን፣ ላጲስ መብላት አልነበረብንም እንላለን፤ ቾክ ሊቦንብን አይገባም ነበር እንላለን፤ ስናረፍድ መምህራን ሊቆጡን አይገባም ነበር እንላለን!... እንግዲህ ሽሽታችን እንዲሁ ነው፤ ከራሳችን እየሸሸን የት እንደምንደርስ ብቻ እስኪ መጪውን ጊዜ እናያለን፡፡
ይልቁንስ ጀግኖቻችን አገርን አስቀድመው የፈጸሙት ገድል ዛሬ ላይ ላለነው በቁማችን ላንቀላፋን ትውልዶች ዘመቻችን ከባህል ወረራ፣ ከስንፍና ወረረሽኝ፣ ከሱስ፣ ከድህነት ወዘተ... እንድንላቀቅ ጥሪው ደርሶናልና እንንቃ፡፡

አዲሱ ገረመው

Published in መዝናኛ

ጣሊያን በአድዋ ጦርነት የውርደት ካባ ብትከናነብም ከአርባ ዓመት በኋላ ውርደቷን በድል ለመሸፈን ዳግም ኢትዮጵያን ወረረች፡፡ በዳግም ወረራው ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀውን ወራሪ አረበኞች ወደ መሃል ሀገር እንዳይገባ ተከላከሉ፡፡ ተደራጅቶና ክንዱን አጠናክሮ የመጣው ጠላት ግን ታግሎ አሸነፋቸው፡፡ በርካቶችም መስዋት ሆኑ፤ ቀሪዎቹም ቁስለኛ ሆነው ወደ መሃል ሀገር ተመለሱ፡፡ ይሁን እንጂ «የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ» ሆኖ ነገሩ ቁስለኛ ሆነው ወደ መሃል ሀገር የተመለሱ አርበኞች በጣሊያን አጠራር «ሽፍቶች» ፋታ ነሱት፡፡
እኒያ ጣሊያንን ለአምስት ዓመታት ፋታ የነሱትና ድል ያደረጉት የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች የድላቸው ቀን ነገ በደማቅ ሁኔታ የሚከበር ሲሆን፤ በወቅቱ የችግሩ ቀማሽ የነበሩና በጦርነቱም የተሳተፉ በሕይወት ያሉ ሰዎችን በተለይ በአካባቢያ ቸው የነበረውን የሞት ሽረት ትግል በጥቂቱ ለማስታወስ የዓይን እማኞች ምን ይሉ ይሆን?
ዕድሜያቸው 90 ዓመት ደርሷል፤ አቶ ደለለኝ ደሳለኝ ይባላሉ፡፡ በጣሊያን ወረራ ጊዜ የ10 ዓመት ልጅ ነበሩ፡፡ የትውልድ ቦታቸው ሰሜን ሸዋ ላሎምድር በተባለ አካባቢ ነው፡፡ በወቅቱ አርበኛ አባታቸውና እናታቸው ጠላትን ለመዋጋት በየጥሻውና በየዱሩ ሲንከራተቱ ከእነርሱ ላለመነ ጠል አብረው ማስነዋል፡፡
አርበኞች ጣሊያንን ከሀገር ለማስወጣት በሰሜን ሸዋ አካባቢ ያደርጉት የነበረውን ትግል ሲገልጹ፤ ኢትዮጵያ በየጊዜው ቆስቋሽ ይበዛባታል፡፡ ብዙዎች ለመግዛት ታግለዋል፡፡ ስላልተሳካላቸውም እያፈሩ ተመልሰዋል፡፡ ይህ የሆነው የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች በከፈሉት መስዋት ነው፡፡ በሀገር ጉዳይ ወደኋላ የማይሉ በመሆናቸውና እስከ መጨረሻው በመፋለማቸው ነው፡፡
«ጠላት ጣሊያን አድዋ ላይ ታጥቆ ቢመጣም ተሸንፏል፡፡ ከዚያ በኋላ ዳግም ለመውረር ከአርባ ዓመት በኋላ ዘመናዊ መሣሪያ ታጥቆ የመጣውን ጠላት ለመመከት ብዙ ቢደክምም ማይጨው ላይ አሸንፎ ወደ መሃል ሀገር መግባት ቻለ» የሚሉት አቶ ደለለኝ፤ ቁስለኛው በመሰባሰብ በመጣበት ለመመለስ ማይጨው ድረስ ብንዘምትም አልተሳካል ንም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ «እንዴት መሃል ሀገር ተቀምጦ ይገዛናል?» በሚል መምከር ተጀመረ፡፡ ገሚሱ «ለመዋጋት ምግብና ትጥቅ ያስፈልጋል፡፡ ምን በልተን እንዋጋለን? በርሃብ እናልቃለን» የሚል ሃሳብ ሲያነሳ አብዛኛው «እንኳን መሃል ከተማ ማይጨው ድረስ ሄደን ቆስለናል፤ የሀገራችን አውሬ ይብላን» በማለት ወደ ጫካ መግባታቸውን በትዝታ መነጸር ያስታውሳሉ፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ጠላት ውጊያውን ለማጠናከር የደጃዝማች ከፈለው የእናታቸው ቀዬ በሆነው ጌራ ምድር፣ ልጅ ግዛቸው በላሎ ምድር ሕዝቡን እንዲያጠናክሩ ሲስማሙ አብዛኛው ሰው ከደጃዝማች ከፈለው ጋር ወደ ማማ ምድር አቀና፡፡ ሆኖም ጠላት ግዛቱን እያሰፋ፣ አርበኞች ያሉበትን እንዲያሳዩት ሰዎችን እያሳመነና ባንዳውን እያበዛ ወደ ሰሜን ሸዋ መግባቱን ቀጠለበት ይላሉ፡፡
አርበኞችም እንቅስቃሴያቸውን ሌሊት በማድረግ ጠላት ቀን ሲቀማ የዋለውን ሌሊት ያስለቅቃሉ፡፡ መሣሪያ ይዘርፋሉ፡፡ አካባቢውንም እንዳልነበር ያደርጋሉ፡፡ ይህም መሣሪያ ከጠላት እንዲያገኙና እንዲጠናከሩ እየረዳቸው መምጣት ጀመረ የሚሉት አቶ ደለለኝ፤ በወቅቱ ቤልጅግና ምንሽር የተባሉ ውስን መሣሪያዎች ብቻ በመኖራቸውና ጥቂት ሰዎች ብቻ በመያዛቸው ሲተኩሱ ማን እንደተኮሰም ይታወቅ ነበር ይላሉ፡፡
ጠላት ጣሊያን እንዲያግዙት በማሰብ ለባንዳዎች፣ ተቀባይነት እንዲያገኝ ለሕዝቡና እምነት ለጣለበት ሁሉ ገንዘቡንም ማፍሰስ ቀጠለበት፡፡ ሆኖም ማን እንደሚጠቁም ሳይታወቅ አርበኞች በሌሊት እየመጡ ተደጋጋሚ ጥቃት ማድረሱን ገፉበት፡፡ በዚህ ወቅት ከዚያ በፊት በሀገሬው ሕዝብ የማይታወቅ መለያ መታወቂያ ጣሊያን ለእርሱ ደጋፊዎች መስጠት ጀመረ፡፡ መታወቂያውም «በርሜሶ» የሚባል ሲሆን፤ መታወቂያ ያልያዘ በአካባቢው ማለፍ እንዳይችል ተደረገ፡፡ መታወቂያ የሌላቸው በአካባቢው ሲያልፉ ቢገኙ እንዲገደሉ ታዘዘ፡፡ መታወቂያ የያዘው ካለምንም ፍተሻ ውስጥ ድረስ እየገባ የሚያስፈልገውን ዶሮ፣ እንቁላል፣ እንጨት ይወስዳል፡፡ ይህም ጥይትና ጠብመንጃ ይዞ የሚወጣበትን መንገድ ከፈተ ሲሉ ያስታውሳሉ፡፡
«በርሜሶ» የያዙ ባላገሮች መሣሪያ በማውጣት በድብቅ መሸጥና የውስጥ አርበኛ ሆነው ጫካ ለገቡ አርበኞች ማገዘ ጀመሩ፡፡ የውስጥ አርበኞች አካባቢንና የመሬት አቀማመጡን በማጥናት ቀጣይ ያለው ፕሮግራም ምን እንደሚመስል ሙሉ መረጃ በመስጠት ለአርበኞች ማድረሱን እያጠናከሩ መጡ፡፡ በወቅቱ የውስጥ አርበኞች «ቃፌር» የተባለ የመረጃ አደረጃጀት ስለነበራቸው በቃፌሩ አማካኝነት መረጃ ለአርበኞች ይደርስ ነበር፡፡
የጠላት እንቅስቃሴ ሲኖርና ጠላት ወደ አካባቢው እንደሚመጣ ለማስረዳትና ዝግጁ ሆነው እንዲጠብቁ ለመጠቆም ቃፌሩ ወደ አርበኞች በመንቀሳቀስ «ከብቶቹ አልቀት እንዳይጠጡ ወደዚያ በላቸው» እያለ ከተራራ ጫፍ ለተቀመጠው ተወካይ ይገልጽለታል፡፡ እርሱም አርበኞችና ያሉበት አካባቢ በመንገር ጠላትን ለመምታት እንዲዘጋጅ ያደርጋል፡፡ እኔ እየገለጽኩልህ ያለው ያየሁትን የሰሜንሸዋ ትግል ማለትም በመንዝ፣ ላሎ ምድር፣ ማማ ምድር፣ ጌራ ምድር፣ በተጉለትና ቡልጋ፣ ደብረ-ብርሃን፣ ይፋት፣ ደብረሲና ታሰብ መርገጤ የነበሩበት፣ በላሎ ምድር ደጃች አውራሪስ፣ ደጃዝማች አበበ፣ ሁሉም በየአቅጣጫው ተሰልፈው ይታገሉ የነበረበትን ነው፡፡ በላሎ ምድር ወይን አምባ፣ ጦል፣ አረቆ፣ ይገም፣ በጌራ ምድር ሹማች ማርያም፣ ገብርኤል፣ ቀያ ገብርኤል፣ ሙሁዥ፣ ቋች፣ አግረ-መድፊያ፣ ዥገጥ፣ ላንቆት፣ በተባሉ አካባቢዎች ሁሉ ብዙ ሰዎች ማለቃቸውንና እናትና አባታቸው፣ አጎቶቻቸውና ቤተሰብ በሙሉ ከቤት ወጥቶ እርሳቸው ብቻ ከቤት መቀመጥ አለመቻላ ቸው በልጅ ዕድሜያቸው ይህን ሁሉ መከራ ለማየት መገደዳቸውንም ይገልጻሉ አቶ ደለለኝ፡፡
በሰሜን ሸዋ የነበረው ትግል ከባድ ቢሆንም በጥቂቱ ይህ ነው፡፡ የጎንደር፣ የጎጃም፣ ወሎ፣ የትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ሶማሌና አፋር፣ ጉምዝ አላውቅም፡፡ ቀዳማይ ኃይለሥላሴ በውጭ ሆነው እያበረታቱ፣ መላክ ያለባቸውን ድጋፍ እየላኩ አርበኞች ለድል እንዲበቁ ሚናቸው ከፍተኛ ነበር፡፡ እርሳቸው የዲፕሎማሲ ሥራ በመስራት በዓለም መድረክ ተቀባይነት ባያገኙ ጠላትን በአርበኞች ብቻ ማስወጣቱ ይከብድ ነበር ይላሉ፡፡
«ጣሊያንን ከሀገር ለማስወጣት የተከፈለው መስዋትነት ከፍተኛ ነው፡፡ አሁን ሀገሪቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡ ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ ትልቅ አቅም አላት፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ወታደር፣ በየብስ እንዳሻው የሚንቀሳቀስ፣ በአየር የሚወነጨፍ መሣሪያ የጦር ጀቶች ባለቤት ነች፡፡ ለዚህ ሁሉ ድል ግን ትናንት ጀግኖች አርበኞች አባቶቻችን በሁሉም አቅጣጫ የከፈሉት መስዋትነት ነው፡፡ ይህ ትውልድ ይህን ማሰብ አለበት፡፡ አንድነቱን ጠብቆ መጓዝ ያስፈልጋል ሲሉም ያስረዳሉ፡፡
«የዚህ ዘመን ወታደሮች ሁሉም ነገር ተሟል ቶላቸዋል፡፡ በቂ ምግብ ያገኛሉ፣ ትጥቂ እንደፈለጉ ያገኛሉ፣ ደመወዝ አላቸው፡፡ ያን ጊዜ እኮ ምግብ የለም፣ መሣሪያ የለም አንጀታቸውን አስረው ነበር ከጠላት ጋር የሚፋለሙት፡፡ የአሁኑ ወታደር ከእዚህ ታሪክ ብዙ መማር ይችላል፡፡» ሲሉም አቶ ደለለኝ ይመክራሉ፡፡
ልጅ፣ ወጣት፣ እናትና አባት አርበኞች በአንድ ላይ በየሜዳውና በየጫካው የወደቁላት ሀገሪቱ ከጠላት ተጠብቃ ወደ ከፍታ ደረጃ እንድትደርስ፣ በኢኮኖሚም የደረጀችና በዓለም የታፈረች ሀገር እንድትሆን በማሰብ ነው፡፡ ይህ ታሪክ በተገቢው ሁኔታ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ትውልድ ሊማረው ይገባል፡፡ የሕዝቦቿ ማንነት፣ ባህል ሳይበረዝ ሊቆይ የቻለው ዛሬ በተሰራ ታሪክ አይደለም፡፡ ትናንት በሁሉም አካባቢዎች የነበሩ አርበኞች በከፈሉት መስዋትነት ነው፡፡ ታሪክ አይጠቅምም መባል የለበትም፡፡ ካለታሪክ የትም አይደረስም፡፡ የትናንት ማንነቱን የማያውቅ የዛሬ ምንነቱን በትክክል ሊረዳ አይችልም ሲሉም አቶ ደለለኝ ያስረዳሉ፡፡
በኢትዮጵያ ጀግኞች አርበኞች ማህበር የሥራ አመራርና አስተዳደር ምክር ቤት አባል አቶ ዳኛቸው ንጉሴ፤ ጣሊያን፣ ጀርመንና እንግሊዝ ዓለምን ለመቀራመት ባደረጉት ሴራ ኢትዮጵያ ከተያዘች ሌላውን መያዝ ቀላል ነው የሚል እምነት ስለነበ ራቸው ጣሊያኞች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው እሙን ነበር፡፡ በመጀመሪያ ወረራቸው ተሸንፈው ቢመለሱም ከረጅም ጊዜ ዝግጅት በኋላ ተጠናክሮና ዘመናዊ መሣሪያ በመያዝ በባህር፣ በአየርና በየብስ ዳግም መጥቷል፡፡ በወቅቱ ሀገሪቱ ጠቅላይ ግዛት በሚለው የምትተዳደርና መሳፍንትና መኳንንቱ ውስጥ ላይ የእርስ በእርስ የሥልጣን ሽኩቻ ቢኖራቸውም ለውጭ ጠላት አይበገሩም ነበር፡፡
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኞች አርበኞች ማህበር የሥራ አመራርና አስተዳደር ምክር ቤት አባል አቶ ዳኛቸው ተመስገን፤ ጀግኞች አርበኞች ሀገሪቱ አንድነቷን ጠብቃ እንድትኖር፣ ሀብቷ እንዳይመ ዘበርና ባህሏ እንዳይበረዝ ከፍተኛ መስዋትነትን ከፍለውላታል፡፡ ምንም እንኳ ውስጣዊ የሥልጣን ሽኩቻ ቢኖርና እርስ በእርስ የሚፎካከሩበት ሁኔታ የነበረ ቢሆንም፤ በሀገር ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ አቋም ያላቸው በመሆኑ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በየጥሻውና በየጫካው ዱር ቤቴ በማለት ነፃነቷን ሊያስጠብቁ ችለዋል ይላሉ፡፡
በወቅቱ ምንም ዘመናዊ ጦር ሳይኖር፣ የሚበላ ምግብ እንኳ እንደ ልብ ሳያገኙ፣ በድህነት ውስጥ ሆነው በየብስ፣ በባህርና በአየር በዘመናዊ ጦር በመታገዝ ሀገሪቱን ለመቆጣጠር ሲታገል የነበረውን ጣሊያን ድል መቀዳጀት የቻሉት ለግል ጥቅም ብለው ሳይሆን ለሀገር ካላቸው ጽኑ ፍቅርና እምነት በመነጨ ነው የሚሉት አቶ ዳኛቸው፤ በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ በመከላከያ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡ በየብስ፣ በባህርና በአየር እንደልብ ሊንቀሳቀስ የሚችል ዘመናዊ የጦር ባለቤት አላት፡፡ ምንም ሳይኖራቸው ጠብቀው ያቆዩለት ሀገር መሆኗን በማሰብ ለአንድነቷ፣ ለሕዝቦቿ ደህንነትና በምንም መልኩ በውጭ ጠላት እንዳትደፈር ያለባቸውን አደራ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
አሁን ላይ የውጭ ወራሪ የለም፡፡ የሕዝቡ ዋና ጠላት ድህነት በመሆኑ እርሱን ድል ለመምታት ወጣቱ በተሰማራበት ሙያ በቅንነት ሕዝብን ማገልገል አለበት፡፡ ሙስናን መጠየፍና መታገል ይጠበቅ በታል፡፡ ጀግኞች አርበኞች ሀብቷንም አንድነቷንም ጠብቀው ለማቆየት እንጂ ለግል ጥቅም ብለው የከፈሉት መስዋትነት አልነበረም፡፡ በዚህ ዘመን ያለው ትውልድም መማር ያለበት ይህን ነው፡፡ ራስ ወዳድና ስግብግብ ሊሆን አይገባም፡፡ ይህ ከሆነ አርበኞች ጠብቀው ያስረከቧት ሀገር አደጋ ውስጥ ትገባለች፡፡ ሕዝቦቿ እርስ በእርስ እንዲናቆሩና ወደ አላስፈላጊ ቀውስ እንዲገቡ ያደርጋል፡፡ የአርበኞች ቀን ነገ የሚከበረውም ይህን መልዕክት ለማስተላለፍና ትውልዱ ከእነርሱ እንዲማር ለማድረግ ነው በማለት አቶ ዳኛቸው ያብራራሉ፡፡

ዑመር እንድሪስ

Published in ማህበራዊ

እንደ ኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠር 1888 ዓ.ም ዓድዋ ላይ የቅኝ ግዛት ፍላጎቷን ለማሳካት ኢትዮጵያን የወረራዋ ዒላማ አድርጋ ገስግሳ የመጣችው ኢጣሊያ በኢትዮጵያውያን ልዩና ታሪካዊ አንድነት በተሰጠ ምላሽ የሽንፈት ማቋን ተከናነበች፡፡ ኢጣሊያ ዐድዋ ላይ ድል ከሆነች በኋላ ለአጭር ጊዜ በሰሜን ምሥራቅ አፍሪቃ የምትከተለውን የመስፋፋት ፖሊሲ እንደመግታት ብላው ነበር፡፡ ከሽንፈቱ በኋላ አዲስ የተሾመው ጠቅላይ ሚኒስትር ዲሩዲኒ ቀዳሚው ፍራንችስኮ ክሪስፒ ያራምድ የነበረውን ፖሊሲ ሽሮ ለቅኝ ግዛት ማስፋፊያ የተመደበውን በጀት በግማሽ ቀነሰው፤ ከአድዋ ጦርነት በፊት አንገቱን ደፍቶ የነበረው የፀረ-ኮሎኒያሊስት ቡድን አሁን የልብ ልብ አግኝቶ ኢጣሊያ ከነአካቴው የአፍሪቃን ምድር ለቃ እንድትወጣ ለመጠየቅ ተዳፈረ፡፡ ይህ ሁሉ ግን የቆየው ለአጭር ጊዜ ነበር፡፡
ከእንግሊዝ ቀጥሎ ከኢትዮጵያ ጋር ረጅም የጋራ ድንበር ያሏቸውን ቅኝ ግዛቶች የምታስተዳድረው ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ችላ ብላ መኖር አልቻለችም፡፡ ከዐድዋ ሽንፈት 30 ዓመታት በኋላ ወደ ስልጣን የመጣው አምባገነኑ የፋሺዝም አቀንቃኝ ቤኒቶ ሙሶሎኒ፣ ራሱን እንደ ሮም የቀድሞው ንጉስ ጁሊየስ ቄሳር በመቁጠርና ‹‹የኢጣሊያን ክብር ለዓለም አሳያለሁ›› በሚል የረጅም ጊዜ ተስፋ የቅኝ ግዛት ዘመቻውን ሊያሳካ ላይ ታች ማለቱን ተያያዘው፡፡ ነገሩ ይህ ብቻ አልነበረም፤ ኢጣሊያውያን በውስጥ ችግሮቻቸው ላይ የነበራቸውን ትኩረት ለማስቀየር፣ እየጨመረ ለመጣው የኢጣሊያ ህዝብ የማስፈሪያ ቦታ ለመፈለግ እንዲሁም በአውሮጳ መድረክ የከሸፈበትን የመስፋፋት ፖሊሲ ለማካካስ ቅኝ ግዛትን አማራጭ አድርጎ ተነሳ፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ኢጣሊያ ዐድዋ ላይ የተከናነበችውን ሽንፈት ለመበቀል ሙሶሎኒ ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ አዞረ፡፡
ኢትዮጵያ ታሪካዊውንና አንፀባራቂውን የዓድዋ ድል ከተጎናፀፈች ከ40 ዓመታት በኋላ ፋሺስቱ ቤኒቶ ሙሶሎኒ የሚመራት ኢጣሊያ የዓድዋን ሽንፈት ለመበቀልና የኢጣሊያ ምስራቅ አፍሪካ ቅኝ ግዛት ዓላማዋን ለማሳካት ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ታጥቃ ኢትዮጵያን ለመውረር ተዘጋጀች፡፡ ‹‹የታላቋ ሮምን ዝናና ክብር እመልሳለሁ›› በሚለው የቤኒቶ ሙሶሎኒ ያልተጨበጠ ተስፋ ለታጀበው ወረራ ጣሊያናውያን የቸሩት ድጋፍ የጋብቻ ቀለበትን ሸጦ መስጠትን ያካተተ ነበር፡፡
ከብዙ ጊዜያት ዝግጅትና የጠብ አጫሪነት እንቅስቃሴዎች በኋላ፣ በ1928 ዓ.ም ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ወረረች፡፡ የፋሺስት ኢጣሊያ የወረራው ስልትና የአገዛዝ ዘመኑም እጅግ አሰቃቂ እንደነበር ለበርካታ ጊዜያት በምሁራን፣ በፖለቲከኞች፣ በጋዜጠኞችና ሌሎች ዓለም አቀፍ የማህበረሰብ ክፍሎች በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ የፋሺስት ኢጣሊያ የጦር ውጊያና አገዛዝ ጭካኔም ሆነ የኢትዮጵያውያን ጀግንነትና መስዋዕትነት እንኳንስ በዐይኑ ለማየት ከቻለው ይቅርና በታሪክ ከሰማውና ካነበበው ሰው ህሊና የሚጠፋ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ ‹‹የዓለምን የሰላም ተስፋ ያጨለመ፣ የዓለም መንግሥታት ማኅበር የያዘውን ዘላቂ የጋራ ሰላምና ፀጥታን የማስፈን ዕቅድ ያፈረሰ አስነዋሪ ተግባር እንዲሁም ዓለም አቀፍ ስነ-ምግባርን ያጎናጸፈ አሳዛኝ ተግባር …›› በማለት የፋሺስት ኢጣሊያን ድርጊት ያወገዘው፡፡
ቤኒቶ ሙሶሎኒ ያሰበውን የወረራ ዘመቻ ያከናወነው በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከተፈጸሙት አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ድርጊቶች መካከል አንዱ የሆነውን የጦር ወንጀል በመፈፀም ነበር፡፡ የፋሺስት ጦር በዓለም አቀፍ ሕግጋት የተከለከሉ የመርዝ ጋዞችን በመጠቀም ኢትዮጵያውያንን ፈጀ፤ ቤታቸው ውስጥ እንዳሉ በር እየተቆለፈባቸው ተቃጠሉ፤እንኳንስ በዓይን ለማየት በጆሮ ለመስማትም የሚከብዱ ሌሎችም በርካታ ግፎች በኢትዮጵያውያን ላይ ተፈጸሙ፡፡
እንዲያም ሆኖ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን በፋሺስት ኢጣሊያ ላለማስገዛት ለአምስት ዓመታት ያህል ከባድና መራራ መስዋዕትነትን ከፍለዋል፡፡ አካላቸው ጎድሏል፤ ስነ ልቦናቸው ተጎድቷል፤ ሕይወታቸው ጠፍቷል፡፡ ከአምስት ዓመታት የጀግንነት ተጋድሎ በኋላም ወትሮውንም ቢሆን ገና እግሩ ኢትዮጵያን እንደረገጠ መቆሚያ መቀመጫ ያጣው የፋሺስት ጦር ከኢትዮጵያ ምድር ተባረረ፡፡
የአምስት ዓመታቱ የኢትዮጵያውያን አርበኞች ተጋድሎ ኢትዮጵያ ነፃነቷን የጠበቀች አገር እንድትሆን ከማስቻሉም በላይ ለወደፊት እድገቷና ብልፅግናዋም ተመንዝረው የማያልቁ ትሩፋቶችን የሚያስገኝ መልካም አጋጣሚ ነበር፡፡ አውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች በፈጠሯቸው ውስብስብ ፓለቲካዊና አስተዳደራዊ መዋቅሮች ምክንያት ዛሬ በሌሎች አገራት የሚስተዋሉት የቅኝ ግዛት ዘመን ቅሪቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት አልተስተዋሉም ነበር፡፡
ለአብነት ያህል ዛሬ በሀብት ክፍፍል ኢ-ፍትሐዊነት ምክንያት ደም አፋሳሽ ግጭቶች እንዲሁም የሌሎች አገራት ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች የሚስተዋሉባቸው የአፍሪካ አገራት ልክ እንደኢትዮጵያ ሉዓላዊነታቸውን አስከብረው ቢሆን ኖሮ ይህ ቂምና ቁርሾ ላይፈጠር ይችል ነበር፡፡ ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ስርዓት ከተላቀቀች በኋላም እስካሁን ድረስ በሀብት ክፍፍል ኢ-ፍትሐዊነት ምክንያት ግጭቶች በዚያች ሀገር የተለመዱ ሆነዋል፡፡ ዚምባብዌ ሮበርት ጋብርኤል ሙጋቤን መሪዋ አድርጋ በሰየመች ማግስት መሬትን ከነጮች ነጥቃ ለጥቁሮቹ በመስጠቷ ምክንያት የደረሰባትን መገለልና ጫና ዓለም የሚያውቀው ሀቅ ነው፡፡ ቅኝ ገዢዎች በአፍሪካውያን መካከል የፈጠሩት መጠራጠርና ጥላቻ ጠባሳው ዛሬም ድረስ ለደም መፋሰስ ምክንያት ሆኖ የበርካታ አፍሪካውያንን ሕይወት እየቀጠፈ ነው፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ ግን ነገሩ ከዚህ የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ወታደራዊው የደርግ መንግሥት ለ‹‹መሬት ላራሹ›› ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት መሬትን ሲያከፋፍል ጣልቃ የገባበት የውጭ ሀይልም ሆነ እጁን ሊጠመዝዘው የሞከረ ቅኝ ገዢ አካል አልነበረበትም፡፡ የፋሺስት ኢጣሊያ አስተዳደር በኢትዮጵያውያን መካከል ለመፍጠር የሞከረው የጥላቻና የመጠራጠር ሴራም እንዳሰበው ሊሆንለት ሳይችል ቀርቷል፡፡ (ነገር ግን የፋሺስት ኢጣሊያ አስተዳደር በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ ምንም ዓይነት አሉታዊ ውጤት/ተፅዕኖ/ አልነበረውም ማለት ግን ከሀቅ መራቅ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል) ታዲያ እነዚህ ማስረጃዎች የአምስት ዓመታቱ የኢትዮጵያውያን አርበኞች ተጋድሎ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ብቻ ሳይሆን ለዘላቂ እድገቷም መሰረት ሊሆኑ የሚችሉ ታላላቅ ትሩፋቶች እንዳሉት ያሳያሉ፡፡
ይሁን እንጂ አሁን በተጨባጭ የሚታየው ነገር ለዚያ ክቡር መስዋዕትነት ፈፅሞ የሚመጥን አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ታሪክን ማወቅ እንደሞኝነት የሚቆጠርባት አገር ሆናለች፡፡ ‹‹ሚያዝያ 27 የሚከበረው በዓል ምንድን ነው?›› ተብለው ሲጠየቁ ‹‹በፍፁም አናውቀውም››፣ ‹‹ፋሲካ››፣ ‹‹የላብ አደሮች ቀን››፣ ‹‹የባንዲራ ቀን›› … ብለው የሚመልሱ ሰዎች ቁጥራቸው እጅግ የበዛ ነው፡፡ አሳዛኙ ብሎም አስፈሪው ነገር ደግሞ እንዲህ ዓይነት ምላሾች ‹‹የአገር ተረካቢ ናቸው›› ከሚባሉት ከበርካታ ወጣቶች መሰማታቸው ነው፡፡ ታሪኩን በዝርዝር ማወቅ ይቅርና የአርበኞች ድል መታሰቢያ መቼ እንደሚከበር እንኳ ማወቅ ለወጣቶቹ ከባድ ሆኖባቸዋል፡፡
ድሉ ያስገኘልንን ትሩፋቶች እየመነዘርን መጠቀም ሲገባን ታሪኩን አሽቀንጥረን ጥለን የማንነት ቀውስ ውስጥ ገብተናል፡፡ ‹‹ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል›› እንዲሉ፣ ቅኝ ገዢዎች በሌሎች አገራት የፈጠሩት ችግር ኢትዮጵያ ውስጥ በዚያ ልክ አለመኖሩን እንደትልቅ በረከት መጠቀም ሲገባን እኛ ግን ማድረግ አልቻልንም፡፡ ለዚህ አሳፋሪ ጥፋት አንድን አካል በብቸኝነት መጠየቅ ተገቢ ባይሆንም ‹‹ሁሉም ተጠያቂ ነው›› እየተባለ እስከመቼ እንደሚዘለቅ ግን አይታወቅም፡፡
ታሪኩን የማያውቅ ሕዝብ ዛሬን መሻገር አይችልም፤ ከተሻገረም የነገ መድረሻውን በሚገባ አያውቅም፡፡ ታሪኩን የማያውቅ ወጣት ማፍራት ደግሞ ሀገራዊ ስጋት እንጂ እድል አያመጣም፡፡ ዛሬ የዓለምን ምጣኔ ሀብትና ፖለቲካ በበላይነት የተቆጣጠሩትን አገራትን ብንመለከት ለታሪካቸው ያላቸው ክብር ላቅ ያለ ነው፡፡ በጎ ታሪካቸውን አጠንክረውት መጥፎ የሚባለውም ተምረውበት በሚገባ ተጠቅመውት አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ ስለሆነም በመላ አገሪቱ ቸል የተባለው የታሪክ ትምህርት ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡ በምዕራብ አገራት የመዝናኛ ወሬዎች የተጠመዱት የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃንም ለታሪክ ጉዳዮች ላቅ ያለ ቦታ መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ታሪክን ማወቅ እንደነውርና ወንጀል መቆጠሩ ማብቃት አለበት! ፋሺስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያውያን ላይ የፈፀመው ግፍ ከአዕምሮ የሚጠፋ ድርጊት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ነፃነት ለማስጠበቅ የከፈሉት መስዋዕትነትም አኩሪነቱ የድሉ ባለቤት በሆኑ መላ ኢትዮጵያውያን ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር ይኖራል፡፡ ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለኢትዮጵያ ነፃነት ሰማዕታት!

አንተነህ ቸሬ

Published in ፖለቲካ

ሴቶች ባልተሰማሩበት የሥራ መስክ ውስጥ ነበር የመሥራት ፍላጎታቸው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ የመጀመሪያ ምርጫቸው የአብራሪነት ትምህርት ተምረው በኢትዮጵያ አየር ኃይል ውስጥ ለማገልገል ስለነበር፣ተቋሙ ያዘጋጀውን የመግቢያ ፈተና ለመፈተን ለምዝገባ ቀረቡ፡፡ተቋሙ ግን ተስፋ የሚያስቆርጥ ምላሽ ሰጥቶ አሰናበታቸው፡፡ በወቅቱም በማፌዝ ምላሽ የሰጧቸው ሰው ሁኔታ የሚያበሳጭ እንደነበር ያስታው ሳሉ፡፡ አሁንም ሌላ ሴቶች ያልተሳተፉበትን የትምህርት ዘርፍ ፈልጉ፡፡ ቆይተው ግን የከብት ህክምና ትምህርት መስክ አገኙ፤ ዶክተር ዓለምፀሐይ ተስፋዬ፡፡
በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ነቀምቴ ለሥራ ጉዳይ በነበርኩበት ጊዜ ያገኘኋቸው ዶክተር ዓለም ፀሐይ ተስፋዬ በእርሳቸው ዘመን ደክመው ያገኙት የትምህርት ዕድል ዛሬ ብዙ ሴቶች የሚማሩበት መሆኑ ከእርሳቸው የትምህርት ዘመን በኋላ ለውጦች መኖራቸውን በአድናቆት ይገልጻሉ፡
ዶክተር ዓለምፀሐይ እንዳጫወቱኝ የእንስስሳት ህክምና ትምህርት ዕድሉን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደብረዘይት የእንስሳት ህክምና ፋካልቲ ነበር ያገኙት፡፡ ከሁለት ዓመት የትምህርት ቆይታ በኋላ በከብት ህክምና በዲፕሎማ ተመርቀው በኦሮሚያ ክልል ሰበታ ከተማ በሚገኘው ስቴላ በተባለ የወተት ሀብትና የከብት እርባታ ድርጅት ውስጥ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡ ባለቤታቸው የውጭ የትምህርት ዕድል አግኝተው አብረው ወደ ፊንላንድ ሀገር ሲሄዱ ነው ሥራቸውን የለቀቁት፡፡ ውጭ ሀገር መሄዳቸው ሙያቸውን የበለጠ ለማሳደግ መልካም አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል፡፡ ፊንላንድ በሚገኘው ሂልሲንኪ ዩነቨርሲቲ በእንስሳት ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ እ.ኤ.አ.በ1982 አገኙ፡፡ በወቅቱም በጥሩ ውጤት ትምህርታቸውን በማጠናቀቃቸው የተማሩበት ዩኒቨርሲቲ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል ሰጥቷቸው በዘርፉ ዶክተር ደረጃ ለመድረስ በቅተዋል፡፡
ዶክተር ዓለምፀሐይ ትምህርታቸውን እንዳጠና ቀቁም ዩኒቨርሲቲው ቀጥሯቸው በመምህርነት አገልግለዋል፡፡ ከብቶች ምን ዓይነት መኖ መመገብ እንዳለባቸው፣ ምግቡ የወተት ምርታቸውን ለመጨ መር ያለው እገዛ፣ የወተት ምርቱ በሰው ጤና ላይ የሚያስከትለው ጉዳትና የሚያስገኘው ጥቅም እንዲሁም ለወተት ሀብት ልማት ዕድገት እንቅፋት የሆኑ ነገሮች ምን እንደሆኑ በተለይም በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች ላይ ትኩረት አድርገው ያስተምሩ እንደነበርና በዘርፉ የተለያዩ የምርምር ሥራዎች መሥራታቸውን ነግረውኛል፡፡ የምርምር ሥራዎቻ ቸውንም በሀገሪቱ በሚገኘው «ቬትሪነሪ ኤንድ ፉድ ሳይንስ ኢኒስቲትዩት» በተባለ የትምህርት ተቋም ውስጥ ነው የሠሩት፡፡ የምርምር ሥራዎቻቸውም በምርምር መፅሔት ( ጆርናል) ላይ ታትሟል፡፡
ዶክተር ዓለምፀሐይ በትምህርትና በምርምር ያካበቱትን እውቀት እንዲሁም የሌሎች ሀገሮች የወተት ሀብት ልማት ተሞክሮን ይዘው ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ለመሥራት የመጡት፡፡ ሀገራቸው ገብተው እንዲሠሩ የእናታቸው ግፊት ከፍተኛ እንደነበርም ይናገራሉ፡፡ እርሳቸውም ሳያቅማሙ ነበር የውጭ ሀገር ኑሯቸውን ትተው ሀገራቸው የተመለሱት፡፡
ዶክተር ዓለምፀሐይ የወላጆቻቸውን ቦታ ህጋዊ አድርገውና ፈቃድ አውጥተው የተሻሻሉ የወተት ላሞችን ማርባት ጀመሩ፡፡ እቅዳቸው ከአካባቢው ህብረተሰብም ወተት ሰብስበውና አቀነባብረው ለተጠቃሚው ለማቅረብ ነው፡፡ ወተት ማቀነባበር ያለውን ጥቅም በተመለከተም እንዳስረዱት በሙቀት ( ፓስቸራይዝድ ) በማድረግ ከሰው፣ከእንስሳና ከአካባቢ ብክለት ወደ ወተት የሚተላለፍ ጀርም እንዲሞት በማድረግ የጤና ጉዳት እንዳይከሰት ቀድሞ ለመከላከል ይረዳል፡፡ ወተትን በማዕከል ተጠቃሚው ጋ ማድረስ ለተጠቃሚው ጤና መጠበቅ እጅግ ጠቃሚ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ወተትን በተለያየ ጣዕም ለሕፃናት፣ለህሙማንና በተለያየ ዕድሜ ላይ ለሚገኝ ሰው ተስማሚ አድርጎ ማቅረብ የሚያስችል ቴክኖሎጂ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
እርሳቸው እንዳሉት ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ አንድ ሰው የወተት ላሞችን አርብቶ፣የተሻሻሉ ዝርያዎችን አቅርቦ፣ለላሞቹ መኖ አዘጋጀቶ፣ወተት አቀነባበሮ፣ገበያ አፈላልጎ፣ ተጠቃሚው ጋ አድርሶ የሚያዋጣና የማይቻል በመሆኑ ፣ በእያንዳንዱ ዘርፍ ላይ የሚሠራ ሰው ያስፈልጋል፡፡ ሥራው ሲከፋፈል በዘርፉ ውጤታማ የሆነ ሥራ ይሠራል፡፡ ለብዙ ሰውም የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡
ወተት ማለብ ሙያ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ዓለምፀሐይ በሌሎች ሀገሮች ትምህርት እንደሚሰጥና በዘርፉ ተማሪዎች እንደሚመረቁ ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን የታሰበም እንዳልሆነ ካለው ነባራዊ ሁኔታ መረዳታቸውን ይናገራሉ፡፡ ቴክኒክና ሙያ የሚያሠ ለጥኑ የትምህርት ተቋማት በመስኩ ባለሙያ ማፍራት እንደሚችሉም ገልጸዋል፡፡ በወተት ልማት ለውጥ ማምጣት ከተፈለገ ግን ለዘርፉ የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ መመቻቸት እንዳለበትና በሠለጠነ ባለሙያ መመራት እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡
በወተት ልማቱ ላይ ከተሰማሩ ጀምሮ በባለሙያ፣ በመኖ አቅርቦት ችግር ፣የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ ባለማድረግ፣ሥራውን የሚያቀላጥፍ ምቹ ሁኔታ ባለመፈጠሩና ተያያዥ በሆኑ ምክንያቶች ያቀዱትን ወተት የማቀነባበር ሥራ አልጀመሩም፡፡ ከጥቂት ገበሬዎች ከሚሰበስቡትና ካሏቸው ላሞች የሚያገኙትን ወተት ለተጠቃሚው በማድረስ ሥራ ላይ ለመወሰን ተገድደዋል፡፡ እርሳቸው የወተት ላሞችን ጨምሮ 45ከብቶች አሏቸው፡፡ ከብቶቹ በሚገኙበት ግቢ ውስጥ የወተት ማቀነባበሪያ ቤት ሠርተዋል፡፡ መሣሪያም ተተክሏል፡፡ወደሥራ ለመግባት ትልቅ እንቅፋት የሆነባቸው ወተት ከአካባቢው ገበሬ ሰብስቦ ወደማቀነባበሪያው ለማድረስ ጊዜያዊ የመሰብሰቢያ ቦታ አለማግኘታቸው ነው፡፡
ማዕከል በሆኑ ጊዜያዊ የመሰብሰቢያ ቦታዎች ማቀዝቀዣዎች በመትከል ወተቱ እንዲሰበሰብ ነበር እቅዳቸው፡፡ የመስሪያ ቦታ እና ለመኖ ማዘጋጃ መሬት ጥያቄ ለዞኑና ለከተማ አስተዳደሩ ቢያቀርቡም ነገ ዛሬ እየተባሉ በመመላለስ ዓመታት ተቆጥሯል፡፡ ዶክተር ዓለምፀሐይ አነስተኛና ከፍተኛ አምራቾችን የያዘ 40አባላት ካለው «ሮብሰን የወተት አምራቾች» ከተባለ ማህበር ጋር በጋራ ቢንቀሳቀሱም ለስኬት አልበቁም፡፡ማህበሩ ከዞኑ እውቅና አግኝቶ ከተመሠረተ አምስት ዓመታት ተቆጥሯል፡፡
ወተቱ ከአርሶአደሩ ተሰብስቦ ወደአንድ ማዕከል ገብቶ ተቀነባብሮ እንዲቀርብ ካልተደረገና የጋራ ተጠቃሚ መሆን ካልተቻለ በማህበር መደራጀቱ ትርጉም እንደሌለውም ዶክተር ዓለምፀሐይ ይናገራሉ፡፡ ጥያቄያቸው ምላሽ እስኪያገኝ የማህበሩ አባላት በግላቸው በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ዶክተር ዓለምፀሐይ እንዳሉት በአካባቢው የመኖ አቅርቦት የለም፡፡ ከሰበታ ከተማ እየገዙ ነው የሚጠቀሙት፡፡ መኖውም ለከብቶቹ በሚስማማ ባለሙያ ባለመዘጋጀቱ እርሳቸው የተለያዩ መኖዎችን ጨምረው በማዘጋጀት ነው ለከብቶቻቸው የሚሰጧቸው፡፡ መኖ የከብቶቹን ሥጋ እና የወተት ላሞችን ምርት መጨመር መቻል አለበት፡፡ ገበያ ላይ ያለው መኖ ግን የሚፈለገውን የከብቶች መሻሻል እያስገኘ አይደለም፡፡ ሙያው በእጃቸው ስለሆነ ለከብቶቻቸውም የህክምና ክትትል በማድረግና በማዋለድ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ያደርጋሉ፡፡ ከአቅም በላይ ሲሆንባቸው ነው ሀኪሞች የሚፈልጉት፡፡ ዶክተር ዓለምፀሐይ ከወጣትነት ዕድሜያቸው ጀምሮ በቆዩበት ሙያ ውጤታማ ለመሆን በደስታ ሥራውን ቢሠሩም ለዘርፉ የሚደረገው እገዛ አነስተኛ በመሆኑ የሚፈልጉትን ያህል መራመድ አልቻሉም፡፡
ዶክተር ዓለምፀሐይ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሙያዊ ድጋፍ ሲጠይቃቸውም አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ ያግዛሉ፡፡ ለልምምድ ወደርሳቸው የሚሄዱ የእንስስሳት ህክምና ተማሪዎችን በማገዝም ሙያዊ ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ ልምዳቸውንም ያካፍላሉ፡፡ ዩኒቨርሲ ቲዎችን የበለጠ ለማገዝ ፈቃደኛ ናቸው፡፡ ተማሪዎች ተመርቀው ሥራ ከመጀመራቸው በፊት በትምህ ርትቤት በተግባር ላይ በደንብ መሥራት እንዳለባቸውም መክረዋል፡፡ በተግባር ለመለማመድ ያለው ፍላጎት በተማሪዎች በኩል አነስተኛ ሆኖ እንዳገኙትም ይናገራሉ፡፡እርሳቸው ሙያቸውን ለትውልድ ማሸጋገርና የጀመሩት ወተት የማቀነባበር ሥራ እውን ሆኖ እርሳቸው በማይኖሩበት ጊዜም እንዲቀጥል ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፡፡

በዶክተር ዓለምፀሐይጋ የወተት ልማት ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው ከሚሠሩት ሠራተኞች መካከል በማታው የትምህርት ክፍለጊዜ እየተማረ ስድስተኛ ክፍል መድረሱን የነገረኝ ወጣት ሙሉጌታ ተስፋዬ የሥራ ዕድል ማግኘቱ ብቻ ሳይሆን ሙያም መቅሰሙን ገልጿል፡፡ ከብቶች በቤት ውስጥ ሆነው እንክብካቤ እየተደረገላቸው የወተት ምርት ሲሰጡ ያየው ዶክተር ዓለምፀሐይ ጋ መሥራት ከጀመረ ወዲህ መሆኑን ነግሮኛል፡፡
ላም በማለብና አትክልት በመንከባከብ ሥራ ለስድስት ዓመታት አብሯቸው የሠራው አቶ ብርሃኑ ጥሩነህም ውሎና አዳሩም በሥራው ቦታ እንደሆነና በደስታ በሥራው ላይ እንደቆየ አጫውቶኛል፡፡ ሙያን እየተማረ በደመወዙ ኑሮውን ማሻሻል እንደቻለም ገልጿል፡፡
ዶክተር ዓለምፀሐይ ላነሷቸው ቅሬታዎች የነቀምቴ ከተማ ህብረት ሥራ ማህበር አደረጃጀት ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ ገመቹ እንደገለጹት በከተማዋ በወተት ልማት ላይ የተሰማሩት ተሰባስበው ባቀረቡት የመደራጀት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝተው በማህበራት ማደራጃ አዋጅ መሠረት ተደራጅተዋል፡፡ ስለማህበር አደረጃጀት ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተደርጎ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ፈቃድ አግኝተዋል፡፡ ማህበሩ ባደረገው እንቅስቃሴ በተለይም ዶክተር ዓለምፀሐይ ለአካባቢው አርሶአደር በተመጣጣኝ ዋጋ መኖ በማቅረብና ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ እገዛ እያደረጉ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ማህበሩ የጠየቀውን የገበያ ቦታና የመኖ ማዘጋጃ መሬት ያላገኙበትን ምክንያት አቶ ምትኩ እንዳስረዱት ከመሬት ፖሊሲ ዝግጅት ጋር በተያያዘ ጥያቄው ምላሽ ሳያገኝ ዘግይቷል፡፡ ጥያቄው ከቢሮው አቅም በላይ በመሆኑ ሊፈፅም አልቻለም፡፡ ቢሮው ጥያቄያቸውን ለሚመለከተው አካል በማቅረብና ያለውን ሁኔታም ተከታትሎ ጥያቄያቸው ምላሽ እንዲያገኝ አብሯቸው ለመሥራት ዝግጁ ነው፡፡ እየሠራም ይገኛል፡፡ ቢሮው የሚጠበቅበትን በማድረግ ዘርፉ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ እንደሚሠራም አቶ ምትኩ ገልጸዋል፡፡
ዶክተር ዓለምፀሐይ ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ ጋርም እየሠሩት ስላለው ሥራ በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሂርጳ ለገሠ እንዳስረዱት ዩኒቨርሲቲው ዘግይቶ ነው ያወቃቸው፡፡ ካወቃቸው በኋላም በሙያዊ መድረኮች ላይ ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ተደርጓል፡፡ በፕሮጀክት ቀረፃ ላይም እገዛ አድርገዋል፡፡ ለልምምድ ተማሪዎችን ወደእርሳቸው ይልካል፡፡ ወደተግባር ባይገባም ተመራቂ ተማሪዎችን በማማከርና በመምህርነትም እንዲያግዙ ዩኒቨርሲቲው ተነጋግሯል፡፡ ዩኒቨርሲቲውን እንዲያግዙ የታመነ ባቸው በመሆናቸው አብሯቸው ለመሥራት ማቀዱንም ገልጸዋል፡፡ የድጋፍ ደብዳቤም ካስፈለገ ዩኒቨርሲቲውን በማገዝ የሚያደርጉትን አስተዋፅኦ በመግለጽ ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ እንደማያ ስቸግርም አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብቷ ከአፍሪካ አንደኛ ፣ከዓለም አስረኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ እውነታው ይህ ሆኖ ግን የተጠቃሚውን ፍላጎት የሚያሟላ ምርት እየቀረበ አለመሆኑንና ዛሬም ስለወተት እጥረትና ዋጋው ውድ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ ሰሞኑን ደግሞ መባባሱ በተጠቃ ሚዎች ቅሬታ እየቀረበ ነው፡፡ ለችግሩ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ከውጭ በሚገቡ የዱቄት ወተት ላይ ጥገኛ መሆን አመራጭ ተደርጓል፡፡ ሌሎች የወተት ምርታቸው ተትረፍርፎ በዱቄት እያዘጋጁ ለገበያ ሲያቀርቡ ኢትዮጵያ ሀብቱ እያላት የዜጎችዋን ፍላጎት እንኳን ማሟላት አለመቻሏ በብዙዎች ዘንድ ቁጭት አሳድሯል፡፡ የወተት ጉዳይ «የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው» እንደሚባለው ዓይነት እየሆነ ነው፡፡
በቅርቡ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣21ኛ መደበኛ ስብሰባው የቀደሞ የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ሚኒስቴርና የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ተዋህደው የግብርናና የእንስሳት ሀብት ሚኒስቴር ሆኖ እንዲሠራ ውሳኔው ከመፅደቁ በፊት ሁለቱ ተቋማት አንድላይ እንዲሆኑ መደረጉ ለእንስሳት ሀብት የሚሰጠው ትኩረት አናሳ ይሆናል የሚል በአንዳንድ የምክርቤቱ አባላት በቀረበው ስጋት ላይ ሰፊ ውይይት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ እንዲህ ያለው ምክክር ለዘርፉ ትኩረት የተሰጠው መሆኑ ቢታመንም ወደተግባር አልተለወጠም፡፡
ወተት አምራቹንም አገልግሎት ፈላጊውንም ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ምርቱንም በማቀነባበር ብክነትን ለማስቀረት በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችና ትናንሽ አምራቾች የሚያነሷቸው ቅሬታዎች ቢቀረፉ የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል፡፡

ለምለም ምንግሥቱ 

Published in ኢኮኖሚ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን የኑክሌር ስምምነት እንዳይወጡ ጥሪ አቅርበውላቸዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካን እ.አ.አ በ2015 በኢራንና በስድስቱ የዓለማችን ኃያላን አገራት (አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩስያ፣ ጀርመን፣ ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ) መካከል ከተፈረመው የኢራን የኑክሌር ስምምነት አስወጣታለሁ እያሉ እየዛቱ ነው፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊም ሰላም የራቃት ምድር ሌላ ችግር እንዳታስተናግድ ፕሬዚዳንቱ በስምምነቱ ውስጥ እንዲቆዩ ተማፅነዋል፡፡
የኢራን የኑክሌር ስምምነት እ.አ.አ በ2015 ባይፈረም ኖሮ ዓለም ላይ ያንዣበበ ከባድ የጸጥታ ስጋት እንደነበረ ዋና ጸሐፊው ተናግረዋል፡፡ ‹‹የኢራን ኑክሌር ስምምነት እጅግ ወሳኝና ጠቃሚ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ድል በመሆኑ ስምምነቱን የተፈራረሙት አካላት ሊያከብሩት ይገባል፤ የተሻለ አማራጭ ካልተገኘ በስተቀር ፈራሚ አገራት ከስምምነቱ መውጣት የለባቸውም›› ብለዋል፡፡
የዋና ጸሐፊው ሃሳብ የተሰማው ከኢራን ጋር ባላንጣ የሆነችው እስራኤል ስለ ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ግንባታ መርሃ ግብር ያስረዳሉ ያለቻቸውን ‹‹ምስጢራዊ መረጃዎች›› በጠቅላይ ሚኒስትሯ ቤንያሚን ኔታንያሁ በኩል ይፋ ካደረገች ከቀናት በኋላ ነው፡፡ ባለፈው ሰኞ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ቴል አቪቭ ከሚገኘው የእስራኤል መከላከያ መስሪያ ቤት ሆነው የእስራዔል የሥለላና የደህንነት ተቋማት ምስጢራዊ ከሆኑ ቦታዎች አግኝተዋቸዋል ብለው ይፋ ባደረጓቸው መረጃዎች ኢራን ስምምነቱን በመጣስ የኑክሌር ጦር መሳሪያ እየገነባች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ የእስራኤል የሥለላና የደህንነት ተቋማት ከኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ግንባታ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ከ55ሺ የሚበልጡ መረጃዎችን አግኝተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢራን እያከናወነችው ነው ስላሉት የኑክሌር ጦር መሳሪያ ግንባታ ዝርዝር ማብራሪያም ሰጥተዋል፡፡
ሶርያ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ከገባች ወዲህ ደግሞ ኢራን እስራኤልና ሶርያ በሚዋሰኑበት በሰሜን ምስራቅ እስራኤል በኩል ባለው የሶርያ ግዛት ውስጥ ወታደሮቿን ማስፈሯ የሁለቱን ባላንጣ አገራት ፍጥጫ አባብሶታል፡፡
እ.አ.አ በ2015 በኢራንና በስድስቱ የዓለማችን ኃያላን አገራት መካከል የተፈረመውን የኢራን የኑክሌር ስምምነት ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ግንባታዋን እንድታቆምና በምላሹም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በአውሮፓ ኅብረትና በአሜሪካ የተጣሉባት ማዕቀቦች እንዲነሱላት ይደነግጋል፡፡ ኢራን ስምምነቱን የማታከብር ከሆነም ቀደም ባሉት ጊዜያት ከተጣሉባት ማዕቀቦች የከፋ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ተፅዕኖ ያላቸው ማዕቀቦች እንደሚጣሉባት፤ ከዚያም አልፎ ጉዳዩ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እንደሚቀርብ በስምምነቱ ውስጥ ከተካተቱት ድንጋጌዎች መካከል ይጠቀሳል፡፡
ከስምምነቱ መፈረም በኋላም ኢራን የስምምነቱን ድንጋጌዎች ተቀብላ መንቀሳቀስ ጀመረች፡፡ በናታንዝ እና ፎርዶ ጣቢያዎች የሚገኙ ግብዓቶች እንዲወገዱ ተደረጉ፤ በብዙ ቶን የሚቆጠር ዩራኒየም ወደ ሩስያ እንዲወሰድ ተደረገ፡፡ ከዚህ ባሻገርም፣ የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኃይል ተቆጣጠሪ ድርጅት ባለሙያዎች የኢራንን የኑክሌር መሳሪያ ግንባታ በየጣቢያዎቹ ተገኝተው መታዘብ ችለዋል፡፡
ስምምነቱ ሲፈረም አሜሪካን ሲያስተዳድሩ የነበሩት የወቅቱ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ስምምነቱ እንደትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ተቆጥሮላቸዋል፡፡ ኦባማን ተክተው ወደ ነጩ ቤት የመጡት ቢሊየነሩ ዶናልድ ትራምፕ ግን ስምምነቱን መቀበል ይቅርና ስለስምምነቱ መስማት አይፈልጉም፡፡ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ‹‹የምንጊዜውም መጥፎው ስምምነት›› እያሉ የሚያብጠለጥሉትን ይህን ስምምነት እንደሚሰርዙት ያስታወቁት ገና በፕሬዚዳ ንታዊ የምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ነበር፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ የኢራን የኑክሌር ስምምነትን የማይቀበሉባቸው ምክንያቶች ግለሰባዊ፣ ፖለቲካዊና አገራዊ መሆናቸው በተንታኞች ዘንድ ይገለፃል፡፡ ሰውየው የአሜሪካ ጠንካራ አጋርና ወዳጅ የሆነችውን እስራኤልን ለማጥፋት እቅድ አላት የምትባለው ኢራን የኑክሌር መሳሪያ ታጥቃ ማየት አይፈልጉም፡፡ የልጃቸው ኢቫንካ ትራምፕ ባለቤት የሆኑት አይሁዳዊው ጃሬድ ኩሽነር የፕሬዚዳንቱ ከፍተኛ አማካሪ መሆን ደግሞ ሰውየው ለኢራን ያላቸውን ጥላቻ ያባብሰዋል ብለው የሚናገሩ አካላትም አሉ፡፡ ትራምፕ ለእስልምና ያላቸው ‹‹የጥላቻ አመለካከት›› እስላማዊቷን ሪፐብሊክ ኢራንን ለመጥላት ምክንያት ሳይሆናቸው አይቀርምም ተብሏል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ከ1978/79 እስላማዊው የኢራን አብዮት በኋላ ሆድና ጀርባ ከመሆን አልፈው የጦር መሳሪያ ለመማዘዝ የሚቃጡት አሜሪካና ኢራን ቁርሿቸው ከግለሰብ ስሜት የዘለለ ነው፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከኢራን የኑክሌር ስምምነት የመውጣት አልያም ስምምነቱ ውስጥ የመቆየት ውሳኔያቸውን ከስምንት ቀናት በኋላ ያሳውቃሉ ተብሏል፡፡ ትራምፕ ስምምነቱ ኢራንን ለተወሰኑ ጊዜያት ብቻ ከኑክሌር ማበልጸግ ተግባሯ የሚገታ እንጂ ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ባሊስቲክ ሚሳይሎችን ከማምረት የሚያግዳት አይደለም ብለው ያምናሉ፡፡ እንዲያውም ስምምነቱ ኢራን በውጭ አገራት ባንኮች ያላትንና እንዳይንቀሳቀስ ታግዶባት የነበረውን 100 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ እንዲለቀቅላት ስላደረገ ኢራን ገንዘቡን ሽብርተኞችን ለመደገፍ፣ የጦር መሳሪያ ለመግዛት እንዲሁም አክራሪነትን ለማስፋፋት ተጠቅማበታለች ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
የስምምነቱ ፈራሚ የሆኑ የአውሮፓ አገራት ብሪታኒያ፣ ጀርመንና ፈረንሳይ ግን ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት እንዳትሆን ለማድረግ ስምምነቱን አክብሮ ከመቀጠል የተሻለ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ተስማምተዋል፡፡ ፈረንሳይ ቀደም ባሉት ዓመታት በዓለም ፖለቲካ ሚዛን ላይ የነበራትን ተፅዕኖ ለመመለስ እየተጉ ናቸው የሚባሉት ጎልማሳው ፕሬዚዳንቷ ኢማኑኤል ማክሮን፣ ከሳምንት በፊት ወደ ዋሽንግተን ዲ.ሲ ሄደው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከኢራን የኑክሌር ስምምነት እንዳይወጡ ተማፅነዋቸዋል፡፡ ከውይይታቸው በኋላም አዲስ የኑክሌር ስምምነት ሃሳብ ሊቀርብ እንደሚችልም ፍንጭ ሰጥተው ነበር፡፡
ታዲያ ይህ ሁሉ ሲሆን ኢራንም ዝም አላለችም፡፡ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሮሃኒ «ዶናልድ ትራምፕና ኢማኑኤል ማክሮን አዲስ የስምምነት ረቂቅ የማቅረብ መብት የላቸውም፤ ኢራን አዲስ ስምምነት አትቀበልም›› ብለዋል፡፡ ዶናልድ ትራምፕ ከስምምቱ በመውጣት በኢራን ላይ ማዕቀብ የሚጥሉ ከሆነ ኢራን ከባድ የአፀፋ እርምጃ እንደምትወስድም አስጠንቅቀዋል፡፡
በሌላ በኩል ዶናልድ ትራምፕ ለዘብተኛ ናቸው የሚባሉ የካቢኔ አባሎቻቸውን እያሰናበቱ ልክ እንደርሳቸው ሁሉ የቀኝ አክራሪ ፖለቲካን የሚመርጡ ሰዎችን በዙሪያቸው እያሰባሰቡ ነው፡፡ በቅርቡ በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር መስማማት አቅቷቸው ‹‹ከትራምፕ ጋር መስራት ይብቃኝ›› ብለው የለቀቁትን ሌተናል ጀኔራል ኸርበርት ሬይሞንድ ማክማስተርን ተክተው የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሆነው የተሾሙት ጆን ሮበርት ቦልተን፣ በኢራን ላይ ያላቸው አቋም ለድርደርና ስምምነት ቦታ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ቦልተን ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት ለመሆን የምታደርገውን ሙከራ ለማስቆም እስራኤል የኢራንን ወታደራዊ መሳሪያዎች እንድታወድም ሲገፋፉ ኖረዋል፡፡ ‹‹ለኢራን የተሻለው አማራጭ ስምምነት ሳይሆን ወታደራዊ እርምጃ ነው›› የሚል አቋምም አላቸው፡፡
አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዎም ሰሞኑን፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ይፋ ያደረጓቸው መረጃዎች የኦባማ አስተዳደር ስምምነቱን የፈረመው በውሸት ላይ ተመስርቶ እንደሆነ አመላካች ናቸው›› ማለታቸው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካን ከኢራን የኑክሌር ስምምነት ለማስወጣት ላሰቡት እቅድ አቅም እንደሚሆናቸው ተገምቷል፡፡ ፖምፔዎ ሰሞኑን ወደ መካከለኛው ምስራቅ አቅንተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እንዲሁም ከኢራን የቀጣናው ዋነኛ ተቀናቃኝ ከሆነችው ከሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት ጋር በመከሩበት ወቅት ኢራንን ማብጠልጠላቸው ስምምነቱ እንዲቀጥል ለሚፈልጉ ወገኖች መልካም ዜና አይመስልም፡፡
(የመረጃው ምንጭች ፡- ቢቢሲ እና አልጀዚራ)

አንተነህ ቸሬ

Published in ዓለም አቀፍ

ሀገር ማለት ልጄ፣ ሀገር ማለት፣
እንዳይመስልሽ የተወለድሽበት ቦታ ፣ የተወለድሽበት አፈር፤
እትብትሽ የተቀበረበት ፣ ቀድመሽ የተነፈሽው አየር፤
ብቻ እንዳይመስልሽ።
ሀገር ረቂቅ ነው ቃሉ፤
አገር ውስብስብ ነው ውሉ።
ሀገር ማለት ልጄ ፣
ሀገርማለት ምስል ነው ፣በህሊና የምታኖሪው፤
ከማማ ማህጸን ከወጣሽበት ቀን ጀምሮ ፤
በጠባሽው ጡት፣ ወይም ጡጦ ፣
በዳህሽበት ደጃፍ፣ በወደቅሽበት ፈፋ፤
በተማርሽበት ትምህርት ቤት፣
በተሻገርሽው ዥረት ፤በተሳልሽበት
ታቦት ፣ ወይ በተማፀንሽው ከራማ ፤
በእውቀትሽና በህይወትሽ፣
በእውነትሽና በስሜትሽ ፣
የምትቀበይው ምስል ነው ፣ በህሊናሽ የምታኖሪው፤
ስትወጂ ሰንደቅ ታደርጊው፡፡
ቢያስጠላሽ የማትቀይሪው።
ሀገር ማለት የኔ ልጅ ፣
አማራውና አፋሩ፣ ኦሮሞው ሲዳማው ፣ ጉራጌኛሽን ባይሰማ፤
ያልገባው እንዳይመስልሽ ፣ ሀዘን ደስታሽን ያልተጋራ።
የየልቦናችንን ሀቅ፣ ፍንትው አድርጎ እያሳየ፤
ህዝቦችን ከሰንደቃቸው፣ አስተሳስሮ ያቆየ፡፡
ሀገር ቋንቋ ነው ልጄ፣ የሁለንተናሽ መስታወት፤
ሲከፋሽ ትሸሸጊበት ፣ ሲደላሽ ትኳኳይበት።
የኔ ልጅ ፣
አያት ቅም አያትሽ ፣ሰላም ሲሆን ከወልቂጤ አድማስ ማዶ ሸቅጦ፣
ሲያቀና ወረቱን፤
ለእኔና ለአንቺ መኖሪያ፣ ሲያቀና ቀዬና ቤቱን፤
ሀገር ጠላት ሲደፍራትም፣ ጦሩን ሰብቆ እየፎከረ፤
ከኦሮሞው ከትግሬው፣ ከአፋሩ ከወላይታው፣ . . . ከሁሉም የጦቢያ ልጆች ፣
አጥንቱን እየማገረ፤
ሀገር ይሉት መግባቢያ ፣ሰንደቅ ይሉት መለያ ፣ ሲያቆይልሽ፤
በጉራግኛ ማትገልጭው፣ በጎጥ የማትገድቢው፣ ስንት አለ ታሪክ መሰለሽ!
እና የእኔ ልጅ፣
ለዚህ ነው ሀገር ይሉት ቋንቋ፣ ላንቺ የሚያስፈልግሽ፤
..........
ከሁሉም በላይ ልጄ ፣
ተፈጥሮ ከቸረው በረከት ፣ የላቡን ፍሬ የሚበላ፤
ሀገር ማለት ወገን ነው፣ የእኔ የምትይው ከለላ።
ትመኪበት ጥሪት፣ ትደምቂበት ብርሃንሽ፤
የሰብዕናሽ ግማሽ ውል ፣ወገን ነው ማሕተምሽ፡፡
ዜጋው ነው ልጄ ሀገርሽ።
............................
እና የኔ ልጅ፣
ሀገር ረቂቅ ነው ቃሉ፤
ሀገር ውስብስብ ነው ውሉ።
ከበድሉ ዋቅጅራ ‹‹ሀገር ማለት ልጄ›› (2004 ዓ.ም.) ከታተመው የግጥም መድብል የተወሰዱ ስንኞች ናቸው፡፡
አዎ አገር ማለት በአንድ ቃል የሚገለፅ አይደለም፡፡ ዛሬ ያለው ትውልድ በሙሉ ነፃነት በአገሩ የሰላም አየር የሚተነፍሰው ቀደምት ኢትዮጵያውያን የአገርን ምንነትን አውቀው ባቆዩን ታሪክ ነው፡፡
ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም በኢትዮጵያውያን የተገኘው ድል ከየካቲት 23 በዓድዋ ከተገኘው ድል የማይተናነስ ልዩ ትርጉም ያለው ነው። ቀደምት አባቶቻችን በዱር በገደል ደምና አጥንታቸውን መስዋዕት አድርገው ዛሬ ከቅኝ ተገዢነት ነፃ የሆንንበትን አኩሪ ገድል አጎናፅፈውናል።
የዛሬ 77 ዓመት ጣሊያን ከአድዋ ሽንፈት 40 ዓመታት በኋላ በዘመናዊ የጦር መሣሪያና በወታ ደራዊ ኃይል ይበልጥ ተደራጅታ ኢትዮጵያን ከሦስት አቅጣጫዎች ወረረች፡፡ ከአድዋው ዘመቻ ያልተሻለ የጦር ትጥቅ የነበራት ኢትዮጵያም የጣሊያንን ጦር ለስምንተ ወራት በፅናት ተዋጋች፡፡
ያኔ የወቅቱ ኃያላን አገራት እንግሊዝና ፈረንሳይ የጦር መሣሪያ በግዢ እንዳታገኝ ለጣሊያን ተደርበው ስላሴሩባት ኢትዮጵያ ብቻዋን ጦርነቱን በመጋፈጧ ድል ማግኘት አስቸጋሪ ነበር፡፡
በየግንባሮቹ የሚዋጉት የኢትዮጵያ የጦር አዛዦች ብዙዎቹ ሞተው፣ ሠራዊቱም በአውሮኘላን ቦምብ ተደብድቦ፣በመርዝ ጢስ ተቃጥሎና ያለቀው አልቆ ጣልያን ጊዜያዊ ድል አግኝታ ዋና ዋና ከተሞችን ብትቆጣጠርም ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በገጠሩ ክፍል እምቢ ለአገሬ፣ ለነፃነቴ ብለው የሽምቅ ውጊያ ጀመሩ፡፡ ንጉሰ ነገስቱም ስደት ሄደው በጊዜው ለነበረው የመንግሥታቱ ማኅበር /ሊግ ኦፍ ኔሽንስ/ አቤቱታ ቢያቀርቡም የሚሰማቸው ግን አልተገኘም፡፡
አርበኞች ግን ከቀን ወደ ቀን ድል እየተቀዳጁ የጣሊያን ወታደሮችን መግቢያ መውጫ በማሳጣት ከጣሊያን ወታደሮች በሚማርኳቸው መሣሪያዎች ራሳቸውን እያደራጁ አብዛኛውን የገጠር ክፍል ተቆጣጠሩ፡፡
ወቅቱ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ነበርና ጣሊያን የናዚ ጀርመን አጋር ሆነች፡፡ በዚህ የጣሊያንና የጀርመን ናዚ ወዳጅነት ያልተደሰቱት እንግሊዝ የጣሊያን ጠላት ሆና ኢትዮጵያን ደገፈች፡፡_እንግሊዞች ወታደራዊ ድጋፍ ሰጥተው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ረዷቸው፡፡
በጄኔራል ካኒንግሂም የሚመራው የእንግሊዝ ጦር ከኬንያ ተነስቶ ከደቡብ አቅጣጫ ወደ መሀል ኢትዮጵያ ሲገሰግስ ፤ በጄኔራል ፕላት የሚመራው ጦር ከሱዳን ተነስቶ ወደ አሥመራ ፤ ከዚያም ከሰሜን አቅጣጫ ወደ መሐል ኢትዮጵያ ተንቀሳቀሰ፡፡
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሚመራውና የአርበኞችና የእንግሊዝ አማካሪዎች የሚገኙበት ጌዲዮን ተብሎ የተሰየመው ጦር ከሱዳን ተነስቶ በኦሜድላ አልፎ በጐጃም በኩል ወደ መሐል አገር ገሠገሠ፡፡
የኢትዮጵያ አርበኞችም በጣሊያን ወታደሮች ላይ ጥቃታቸውን አፋፋሙ፡፡_ጣሊያኖች በየቦታው ድል የመሆናቸው ዜና ተነገረ፤_ዘመቻው ከተጀመረ ሁለት ወራት ሳይሞላው ፤ ጣሊያኖች አዲስ አበባን ለቅቀው ወጡ፡፡
መጋቢት 28/1933 ዓ.ም የጄኔራል ካኒንግሃም ጦር አዲስ አበባን ተቆጣጠረ፡፡_ምንም እንኳ እንግሊዞች ኢትዮጵያውን አርበኞች ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ባይፈቅዱም በአርበኞች ተፅዕኖና ቅሬታ የተነሳ ቀዳማዊ ኃይል ሥላሴና አርበኞች ወደ አዲስ አበባ ገቡ፡፡ ንጉሰ ነገስቱም ሚያዚያ 27 በአዲስ አበባ ታላቁ ቤተ-መንግሥት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አውለበለቡ፡፡
በርካታ አፍሪካውያን በነጮች ቅኝ ግዛት ስር ወድቀው መራራውን ጊዜ በሚገፉበት በዚያን ዘመን ጀግኖች አባቶቻችን የቅኝ ገዢዎችን ቅስም በመስበር አገራችን በጠላት ወረራ የማትደፈር መሆኗን ጠንካራ መልዕክት ያስተላለፉበት፣ ለአፍሪካውያንም ኩራት የሆኑበትን ድል የተጎና ፀፉበት ጊዜ ነበር፡፡
ይህ ድል ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እስከ 1960ዎቹ በቅኝ ግዛት ሲማቀቁና፤ ሲጨቆኑ እኛ ግን ከባርነት ቀንበር ነፃ በመውጣት ሰላማዊ አየር እንድንተነፈስ አስችሎናል፡፡ ይህች ታፍራና ተከብራ የኖረችው አገራችንም የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በማቋቋም ሂደት ውስጥ ግንባር ቀደም ተሳታፊ በመሆን ለሌሎች ነጻ መውጣት ጭምር የላቀ አስተዋፅኦ አበርክታለች ፡፡
ይህ ጀግኖች አባቶቻችን የፈጸሙት አኩሪ ታሪክ ነው፡፡ የዛሬው ትውልድ ደግሞ በመለወጥ ላይ ያለችውን አገራችንን ወደ ተሻለ የዕድገት ምዕራፍ በማድረስ አዲስ ታሪክ መፃፍ ይገባዋል፡፡ ዛሬ ግዞተኛ ሊያደርገን ጦር የሚሰብቅብን የውጭ ወራሪ ሃይል የለንም፡፡ ዋናው ጠላታችን ድህነት ነው፡፡ ድል ለማድረግ የምንተጋውም በመቻቻልና በመተባበር መንፈስ ውስጥ ሆነን ድህነትንና ኋላ ቀርነትን በመታገል ነው፡፡
በድህነት ላይ የጀመርነው ዘመቻ አገራችን አድጋና በልፅጋ እስክናያት ድረስ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ የአገራችን ወጣቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ በትጋት ሊንቀሳቀሱ ይገባል፡፡

መዝገቡ ሃይሌ

Published in አጀንዳ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።