Items filtered by date: Saturday, 05 May 2018

በአዲስ አበባ  መንገድ ዳር የተገነቡ ህንፃዎች መንገዶችን ከማጥበባቸው በተጨማሪ ህብረተሰቡን ለአደጋ እያጋለጡ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በባለስልጣኑ የመረጃና ኮሙኒኬሽን ቡድን መሪ አቶ እዮብ በቀለ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንዳሉት፤ በመሀል ከተሞች እንዲሁም በውስጥ ለውስጥ መንገዶች አካባቢ የተገነቡ ህንፃዎች ሲገነቡ ሃያ ሜትር ከዋናው መንገድ ገባ ብሎ መሰራት ያለበት ቢሆንም፣ በተግባር ግን እየታየ አይደለም፡፡ በዚህም የተነሳ እግረኞች በዋናው የአስፋልት መንገድ ላይ እንዲጓዙ ያስገድዳሉ፡፡ ይህ ደግሞ  ነዋሪውን ለአደጋ እያጋለጡ ነው፡፡

እንደ አቶ እዮብ ገለፃ፤ አብዛኛዎቹ ህንፃዎች ሲገነቡ ከመንገድ ዳር ከመሆናቸውም በላይ ምንም ዓይነት ትርፍ ቦታ የላቸውም፡፡ ሆኖም አንድ ባለሀብት ህንፃ ሲገነባ በቂ የመስሪያ ቦታዎች በተለይ ለመኪና ማቆሚያ ሊኖረው ይገባል፡፡ እየተሰሩ ያሉ ህንጻዎች ግን ይህን ታሳቢ  አላደረጉም፡፡ በዚህም በከተማው ውስጥ በአብዛኛው ከእግረኛ መንገድ ቀጥሎ የሚገኙት ምንም ዓይነት ትርፍ ቦታ የሌላቸው ህንፃዎች ናቸው፡፡ 

ባለስልጣኑ የሦስት ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን እንዳለው የሚጠቅሱት አቶ እዮብ፤ ነባር መንገዶች አሁን ያሉበትን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ማስተር ፕላኑን ጠብቆ የማሳደግ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል፡፡ በዚህም  በመሀል ከተማው አብዛኛዎቹ መንገዶች ፈርሰው ድጋሚ እንዲሰሩ በማድረግ ሰባት ሜትር ስፋት ያላቸው መንገዶች መገንባታቸውን በመጠቆምም፤ ቀሪ መንገዶችንም ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አብዛኛው መንገድ ከህንፃው በፊት የተገነቡ በመሆናቸው በመሀል ከተሞች ላይ  እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ሊስተዋሉ እንደሚችሉና አጫጭር መንገዶች ካልሆኑ በቀር ትልልቅ መንገዶች ላይ ችግሩን በሚፈታ መንገድ ማሻሻያ መደረጉን አመልክተዋል፡፡ መንገድ ጠርዝ ድረስ ህንፃ ሲገነባ ፈቃድ የሰጠው አካል በህንፃው አካባቢ ምን ዓይነት መንገድ እንደሚያልፍ ካልተናገረ  ባለስልጣኑ ማስተር ፕላኑ ባስቀመጠው ስፋት መሰረት ተከትሎ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ባለስልጣኑ  መንገዶችን ሲያሰፋ ህንፃዎቹ ሊፈርሱ እንደሚችሉም ገልፀዋል፡፡

መርድ ክፍሉ

Published in የሀገር ውስጥ

በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተቀመጠው የኪራይ ሰብሳቢነትና መልካም አስተዳደር ችግርን የመፍታት ሥራ እጅጉን ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል የተፎካካሪ ፓርቲዎች ተናገሩ፡፡
የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ እንደሚሉት፤ የመልካም አስተዳደርና ኪራይ ሰብሳቢነት ጉዳዮች ኢህአዴግ ገና በእንጭጩ እያለ የተስተዋሉ ናቸው፡፡ ዛሬ ላይ ሰላሳ ሁለት ጥርስ አውጥተው መንከስና ማኘክ ጀምረዋል፡፡ አሁን ባለው ደረጃም ለችግሩ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ስርዓቱ ነው መከሰስና መጠየቅ ያለበት፡፡ ሆኖም የሚስተዋለው ትላልቅ አጥፊዎችን እንኳን መንካት ያልቻለ በትናንሾቹ ላይ ያተኮረ እርምጃ ነው፡፡
አቶ ተሻለ እንደሚሉት፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በዚህ መልኩ ችግሩን ለማቃለል ቆርጠው መነሳታቸው ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡ ነገር ግን ችግሩን መፍታት ማለት አንድን ግለሰብ ህግ ፊት አቅርቦ እንደማስቀጣት ቀላል ያልሆነ የስርዓትን መቀጣትና ማረም የሚጠይቅ ነው፡፡ ከፍትህ አካሉና ከመርማሪ ፖሊሱ ጀምሮ በአንድ ቋት ባለበት ሂደት በኢህአዴግ ውስጥ ተጠያቂነት ያለበት፣ ግልጽና ቅንነት የተሞላበት አሠራርን፤ እንዲሁም ከሙስናና ከመልካም አስተዳደር ችግር የጸዳ ተቋም ለመፍጠርም አይቻልም፡፡ ይህ ደግሞ የተናገሩትን ለመተግበር ያከብድባቸዋል፡፡
ተጠያቂነት ያለው መንግሥት አለመኖር አሁን ላለው የመልካም አስተዳደርም ሆነ ኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ዋናው ምክንያት መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲና ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ ተጠያቂነት የሌለው መንግሥት ሲኖር የመልካም አስተዳደር ችግር ይገዝፋል፤ ኪራይ ሰብሳቢነትም ይንሰራፋል፡፡
አሁን በአገሪቱ ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር ገንኗል፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነትም ሆነ የሙስና ተግባር ስር ሰዷል፡፡ ይሄም አጥፊዎች እንዲታረሙ ባለመደረጉ የተፈጠረ ሲሆን፤ ኢህአዴግም ደፍሮ አጥፊዎችን ሊያርም ያልቻለው ከገንዘብ አልፎ ድምጽ እስከመስረቅ በመድረሱ ነው፡፡ አሁን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀሳብ ደረጃ ለችግሩ መፍትሄና አቅጣጫ ይዘው መቅረባቸው መልካም ቢሆንም፤ ሥርዓቱ የተመሰረተው በዚሁ ላይ በመሆኑ ሥራው በብዙ ጥቅሞች የተሳሰሩና የፈረጠሙ አካላትን ማፍረስን የሚጠይቅ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ጉዑሽ ገብረስላሴ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ አሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ የመንግሥት አካላት የህዝቡን ሀብት እያባከኑ ለራስ ጥቅም ከማዋል ባለፈ የህዝቡን አቤቱታ እየሰሙ አይደለም፡፡ አገልግሎት ላለመስጠትም ቢሮ ዘግተው በመቀመጥ ህዝቡን እያስለቀሱ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ እነዚህ አካላት በተለያዩም ትላልቆቹ አጥፊዎች ተጠያቂ ሲሆኑ አልታየም፡፡ ኪራይ ሰብሳቢዎቹም ሃብት እያፈሩ እንደመሆኑም ጡንቻ ስላወጡ መንግሥትን ሊፈታተኑት ይችላሉ፡፡
እንደ ኃላፊዎቹ ገለጻ፤ ችግሩን ለማቃለል በመጀመሪያ ተጠያቂነት ያለው መንግሥት ሊኖር ይገባል፡፡ ሁለተኛም ህዝቡን በችግሩ ዙሪያ ማወያየትና የትግሉ አካል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ሥራው ከቀደመው የዳር ዳር እርምጃ ወጥቶ ከታች እስከላይ አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብና እርምጃ ለመውሰድ የመንግሥትን ቁርጠኝነት፤ የሁሉምን አካል ተባባሪነትና ደጋፊነትም ይጠይቃል፡፡

ወንድወሰን ሽመልስ

Published in የሀገር ውስጥ

በአትሌቲክስ አፍቃሪዎች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቀው የ2018 የዳይመንድ ሊግ ውድድር የመጀመሪያዋ መዳረሻ ከተማ በሆነችው የኳታሯ ዶሃ ትናንት ምሽት ተጀምሯል። በሁለት ዓመት አንድ ጊዜ ከሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናና በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ከሚካሄደው የኦሊምፒክ ውድድር ሌላ የአትሌቲክስ ውድድሮችን የምንመለከትበት አጋጣሚ ሰፊ አይደለም። ይህም በአገር ደረጃ ሲሆን ነው። በእግር ኳስና በሌሎች ስፖርቶች ፕሪሚየር ሊግ ወይንም በየሳምንቱ የሚከናወኑ ውድድሮች አይጠፉም። ወደ አትሌቲክሱ ስንመጣ ግን የዓለማችንን ስመጥር አትሌቶች ከማራቶን ውድድር ውጪ ያሉትን በግል ሲፋለሙ የምንመለከተው በዓመት በተወሰነ ወቅት ላይ በሚካሄደው በዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ነው።
ዳይመንድ ሊግ በፈረንጆቹ ከግንቦት መጀመሪያ አንስቶ በተለያዩ የዓለማችን አስራ አራት ከተሞች እስከ መስከረም የሚከናወን የአትሌቲክስ ውድድር ነው። ይህ ውድድር በማራቶንና በጎዳና ላይ ውድድሮች የማናያቸውን አትሌቶች የምናይበት ሲሆን በመምና በሜዳ ተግባራት ውድድሮች ላይ ያተኮረ ነው። ይህ ማለት ግን በጎዳና ላይ ውድድሮች ወይንም በአገር አቋራጭ ውድድሮች ላይ የሚካፈሉ አትሌቶች አይወዳደሩበትም ማለት አይደለም።
የዳይመንድ ሊግ ውድድር እ.ኤ.አ ከ2010 ወዲህ መካሄድ የጀመረ ሲሆን ከዛ በፊት እ.ኤ.አ ከ1998 ጀምሮ ጎልደን ሊግ በመባል ነበር የሚካሄደው። ጎልደን ሊግ በአውሮፓ ከተሞች ብቻ የሚካሄድ ውድድር ነበር። ዳይመንድ ሊግ ከተካው ወዲህ ግን ከአውሮፓ ውጪ ውድድሩ ሌሎች አገሮችን አሳታፊ ሊያደርግ ችሏል። የአሜሪካ ሁለት ከተሞች ዩጂንና ኒውዮርክ፤ የቻይናዋ የንግድ ማዕከል ሻንጋይና የኳታሯ ዶሃ ከተማ ጎልደን ሊግ ወደ ዳይመንድ ሊግ ከተቀየረ ወዲህ ውድድሩን በየዓመቱ ማስተናገድ የጀመሩ ከተሞች ናቸው። ይሁን እንጂ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የአሜሪካዋ ኒውዮርክ ተቀንሳ በምትኩ በአፍሪካ የመጀመሪያዋ አገር ሞሮኮ በራባት ከተማ ውድድሩን ለማስተናገድ በቅታለች።
የኳታሯ ዶሃ የዓመቱን የመጀመሪያ የመክፈቻ ውድድር ግንቦት ወር ላይ ስታስተናግድ የቻይናዋ ሻንጋይ ከቀናት ልዩነት በኋላ ሁለተኛውን ውድድር ታስተናግዳለች። ከአስር ቀን በኋላ ደግሞ የጣሊያኗ መዲና ሮም የወሩን የመጨረሻ ውድድር ታዘጋጃለች። ሰኔና ሃምሌ ወር አራት አራት ውድድሮች በተለያዩ ከተሞች ይካሄዳሉ። በአሜሪካ ዩጂንና በሞሮኮ ራባት፤ የኖርዌይ ኦስሎና የስዊዘርላንዷ ሉዛን ሰኔ ላይ ውድድሮችን ያስተናግዳሉ። የፈረንሳይ መዲና ፓሪስ፤ የእንግሊዟ በርሚንግሃም፤ ሞናኮ፤ ስቶክሆልም፤ ለንደን፤ ዙሪክና የቤልጂየሟ መዲና ብራሰልስ የዓመቱን የመጨረሻ ውድድሮች የሚያስተናግዱ ከተሞች ናቸው።
ከወንዶችና ሴቶች የመዶሻ ውርወራ በስተቀር ሰላሳ ሁለቱም ውድድሮች (አስራ ስድስት በወንድ አስራ ስድስት በሴት) እያንዳንዳቸው ሰባት ውድድሮችን ያስተናግዳሉ። በእያንዳንዱ ውድድር አንደኛ ሆኖ የሚያጠናቅቅ አትሌት አራት ነጥብ ሲያዝለት ሁለተኛ የሚሆነው ሁለት ነጥብ፤ ሦስተኛው አንድ ነጥብ ይመዘገብለታል። ይህ የሚሆነው እስከ ዙሪኩ ውድድር ሲሆን በመጨረሻው የብራስልስ ውድድር አንደኛ የሚሆነው አትሌት ስምንት ነጥብ፤ ሁለተኛው አራት፤ ሦስተኛው ሁለት ነጥብ የሚመዘገብለት ይሆናል። ከአስራ አራቱ ውድድሮች አንድ አትሌት ሰባቱን ይወዳደራል። ውድድሮች የሚከናወኑት ጠንካራ ጠንካራ አትሌቶች በተለያዩ ምድቦች ተከፍለው ነው። በሁሉም ውድድሮች አትሌቶች ተመሳሳይ ነጥብ ቢኖራቸው እንኳን በመጨረሻው የብራሰልስ ውድድር ላይ ጠንካሮቹ እርስበርስ ስለሚፎካከሩ የነጥብ አሸናፊውን ለመለየት አይከብድም። በመጨረሻው ውድድር ተመሳሳይ ነጥብ ያላቸው አሸናፊ አትሌቶች ቢኖሩ የዓመቱን የዳይመንድ ሊግ አሸናፊ ለመለየት አንድ አትሌት በስንት ውድድሮች እንዳሸነፈ ይቆጠርና አጠቃላይ አሸናፊው ይለያል። ከሁሉም ውድድሮች ግን ለእያንዳንዱ አትሌት ብራስልስ ላይ የሚከናወነው የመጨረሻ ውድድር ከፍተኛ ነጥብ የሚያስገኝ እንደመሆኑ መጠን ወሳኝ ነው።
ለአንድ የውድድር ዓመት ከሃምሳ ሚሊየን ዶላር ያላነሰ ገንዘብ ይመደባል። ከእዚህ ገንዘብ ውስጥ ስምንት ሚሊየን ዶላር ያህሉ ለአትሌቶች ሽልማት የሚውል ነው። በእያንዳንዱ ውድድሮች አሸናፊ የሚሆነው አትሌት አርባ ሺ ዶላርና ልዩ ሽልማት ይበረከትለታል። የውድድር ዓመቱ አጠቃላይ አሸናፊ በሴትና በወንድ ለየግል «ዳይመንድ አትሌት» የተባለውን ሽልማት የሚወስድ ይሆናል።

ቦጋለ አበበ

Published in ስፖርት

በኢትዮጵያ እግር ኳስ በተለይም ከፍ ባሉት የሊግ ውድድሮች መልካም ዜና መስማት ካቆምን ቆይተናል። ከፌዴሬሽኑ የፕሬዚዳንትና የስራ አስፈፃሚ ምርጫ ውዝግቦች አንስቶ እስከ ደጋፊዎች ግጭትና የስቴድየሞች ሁከት በየእለቱ የምንሰማውና የምናየው ነገር እግር ኳሱን ቁልቁል እየገፋ ገደል ከቶታል። ከዋናው ብሔራዊ ቡድን እስከ ወጣት ብሔራዊ ቡድኖችና በአፍሪካ መድረክ የሚሳተፉ ክለቦቻችን አንዳችም አስደሳች ውጤት ማየት ተስኖናል። አንድ የእግር ኳሳችንን አንገት ቀና የሚያደርግ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ቢኖረንም እሱም ዘወትር ውዝግብ ይዘው በሚነሱት የምርጫና የስፖርታዊ ጨዋነት ጉዳዮች እየተሸፈነ ትኩረት አግኝቷል ለማለት አይቻልም።
በፕሬዚዳንትና ስራ አስፈፃሚ ምርጫ ውዝግቦች የፌዴሬሽኑ ስራ ኃላፊዎች የውሃ ኮዳ ስብሰባ ላይ መወራወር የተጀመረው ኢ- ስነምግባራዊ ድርጊት በስቴድየሞች እስከሚፈጠሩ የደጋፊዎች ግጭት ሲዘልቅ አንድ ያልተባለው ጉዳይ ሄዶ ሄዶ ዳኞች ህግ ባለበት አገር በአሰልጣኝ፤ ተጫዋችና ቡድን መሪ ሜዳ ላይ እየተባረሩ ቡጢ እስከ መቅመስ አድርሷቸዋል። በውጤትና በእግር ኳስ ደረጃችን የተሳለቁብን የውጪ መገናኛ ብዙሃንም በዚህ ድርጊት እግራቸውን አጣምረው እስኪሳለቁብን አሳፍሮናል።
ባሳለፍነው ሳምንት መከላከያ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ባደረጉት ጨዋታ አልቢትር እያሱ ፈንቴ በወልዋሎ አዲግራት የቡድን መሪና ተጫዋቾች የደረሰበትን አሳፋሪ ድብደባ ተከትሎ ሳምንቱ ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር ተያይዞ ትልቅ የመነጋገሪያ አጀንዳ ይሁን እንጂ በእግር ኳስ ሜዳዎቻችን በዳኞች ላይ የሚከሰተው ሞራል የጎደለው ሰብዓዊ ያልሆነ ወንጀል አዲስ አይደለም።
የዳኞች ምሬት አሁን ላይ ገንፍሎ ወጥቶ ባለፈው ረቡዕ ባደረጉት አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ለቀጣዮቹ ሦስት ሳምንታት ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠው የትኛውንም ጨዋታ ላለመዳኘት መወሰናቸው ይታወቃል። በቀጣዩ ቀን ደግሞ ፌዴሬሽኑ የፕሪሚየር ሊጉን አስራ ስድስት ክለቦች ሰብስቦ በጉዳዩ ላይ አወያይቶ ሲያበቃ ዳኞቹ ያሳለፉትን ውሳኔና ያቀረቡት ጥያቄ በሂደት እየተመለሰ ጨዋታዎች እንዲካሄዱ ለመደራደር አስቧል። በሌላ አገላለፅ የዳኞቹን አቋም ፌዴሬሽኑ በይደር ተመልክቶ ታል። ይህ ግን እስከ መቼ ?። በሂደት ማለትስ እንዴት ነው። በእግር ኳሱ ስርዓት አልበኝነት ከደጋፊ አልፎ ምሳሌ ይሆናል ተብሎ በሚጠበቅ ቡድን መሪ በወንጀል ጭምር የሚያስጠይቅ ፀያፍ ተግባር እየተፈጠረ የዳኞችን ጉዳይ በይደር ትቶ ጨዋታዎች እንዲቀጥሉ ማሰብ ምን እንዳይቀርብን ነው?። ጨዋታዎቹ ይቀጥሉ ቢባልስ ነገ ተመሳሳይ ችግር ላለመፈጠሩ ምን ዋስትና ይኖረናል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በመቋረጡ ጦሙን የሚያድረው ተጨዋቹ ነው። አሰልጣኙ ነው። የክለብ አመራር እና የፌደሬሽን አመራሩ ነው። የሚገርመው ነገር ለዚህ ሁሉ ነገር መነሻ የሆኑትም በዋናነት እነዚህ አካላት ናቸው። በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ውድድር መኖርም ሆነ አለመኖር ደጋፊው ምንም የሚያጣው ነገር የለም። ወትሮም ያገኘው ነገር የለምና። አንድ ክለብ በአንድ የውድድር ዓመት ቢያንስ ከሃያ እስከ ሃያ አምስት ሚሊየን ብር እያወጣ ቻምፒዮን ቢሆን እንኳን ከመቶ ሺ ብር ያልበለጠ ሽልማት በሚያገኝበት እግር ኳስ የህዝብ ገንዘብ ከመዝራት የዘለለ ስፖርቱ ላይ አንዳች ጠብ ያለ ነገር አይታይም። ይልቁንም በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ የሚወጣባቸው ተጫዋቾች (ሁሉንም ባይወክልም) ዳኞችን ሲደበድቡና ደጋፊውንም ለፀብ ሲያነሳሱ የህዝብ ንብረት የሆኑ የስቴድየም ቁሶች ሲሰበሩ ማየት ደንብ እየሆነ ነው። ታዲያ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ፕሪሚየር ሊጉ መካሄዱ የግድ መሆኑ ምን ሊያተርፍልን ነው?። ከጨዋታዎቹ መቀጠል ይልቅ አሁን የደረስንበት አስከፊ ደረጃ አሳሳቢ ይመስላል። ፌዴሬሽኑም ቢሆን በብዙ መንገዶች እየጨቀየ ያለውን እግር ኳስ መስመር ለማስያዝ በሩን ዘግቶ ማሰቢያ ጊዜው ከዚህ የበለጠ ከየት ሊመጣ ነው?።
ያደለው አገር በእግር ኳስ ተጫዋቾች ምክንያት የጥይት ባሩድ ብቻ በሚሸትበት አገር ሁለት ባላንጣ ፓርቲዎችን አስተቃቅፎ በእግር ኳስ ያገኘውን ዝና ለሰላም ይጠቅምበታል ፤ በጣም ያደለው እግር ኳስ ዳኛ ደግሞ በሜዳ ላይ በሰራው ጀብድ በአገሩ ህዝብ እምነት በማግኘት በመጨረሻው የስልጣን እርከን ላይ ተቀምጦ አገር ይመራል። ምክንያቱም እግር ኳስ ነጭ እና ጥቁር የሆነ ክብ ቂሪላ ከማንከባለል በዘለለ በምንኖርበት ክብ ምድር ላይ በጎ ተፅዕኖ የማሳደር ትልቅ አቅም አለው፡፡

ቦጋለ አበበ

Published in ስፖርት
Saturday, 05 May 2018 18:46

መወጠኑ አይከብድም

ወላዋይ ምንም ማለት ይሆን? በአላማው የማይጸናስ? ለነገሩ አንተገብረውም እንጂ «የማትጨርሰውን ነገር አትጀምር» ሲባል እየሰማን ነበር ያደግነው። እናንተዬ በኛ ሀገር ያልተጀመረ ነገር ይኖር ይሆን ? ለመጀመሪያ ጊዜ፣ በቁርጠኝነት ምናምን እየተበላ ነው ሁሉ ነገር በሞራል የሚጀመረው። የሚዘልቀው ጥቂቱ ብቻ ነው። ለምን? ሲባል ስራው የተሰጠው አካል ቁጭ ብሎ፣ የተነሳሽነት መቀዛቀዝ፣ የቁርጠኝነት አለመኖር፣ የህዝብ ተሳትፎ መዳከም... ብቻ ምን አለፋችሁ ስራ እንጂ መልስ አይጠፋም።
ያጋጣሚ ነገር ነው። የቅርብ የምላቸው ጓደኞቼ በሙሉ የሚኖሩት ከአዲስ አበባ ውጪ ነው። አንዱ ሰሞኑን መጥቶ ልሸኘው ወደ አውቶቡስ ተራ ብቅ አልኩ። እዚያ ቦታ ለ'ኔ አዲስ የሆነና ደስ የሚያሰኝ ጅምር ተመልክቼ ነበር። መቼ እንደተጀመረ ግን አላወኩም። የአንድ መስኮት አገልግሎት ይሉታል። በተመደቡት መኪናዎች ልክ በየትኛውም የትኬት መሸጫ ወደ ፈለጉት ቦታ ትኬት መቁረጥ የሚያስችል ስርአት ነው። ነገሩ ጥሩ ጅምር ቢሆንም ትንሽ ቆይቶ ረፋዱ ላይ በፐርሰንት እያሉና አንዳንዶቹም እየተሯሯጡ የሚቆርጧት ትኬት ግን መፈተሽ ያለባት ይመስለኛል። የነገሬ ማጠንጠኛ ግን ከአውቶቡስ ተራ መልስ ነው። ጓደኛህስ? ለሚለኝ በሰላም ሸኝቼው በሰላም ገብቷል።
ከአውቶቡስ ተራ የያዝኩት ታክሲ በአትክልት ተራ ሲያልፍ አፍንጫዬ አንዳች መልእክት አገኘ። ይህ ቦታ ለረጅም አመታት አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ አትክልት ሲሸምትበት ኖሯል። ቦታው ለእለት ፍጆታ ከሚፈልጉ እናቶች የተለያዩ ዝግጅቶች እስካለባቸው ደጋሾች፣ ለሆቴልና ለጭማቂ ቤት ከሚገበዩ ነጋዴዎች በየመንደሩ እስከሚቸረችሩ ባለ ጉሊቶች የአትክልትና ፍራፍሬ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል። አትክልት ተራ ይሄ ውለታው እንዳለ ሆኖ አፍንጫ ከሚሰነፍጠው መጥፎ ጠረኑ ባለፈ በተለያዩ ችግሮች የተተበተበም ነው። ለነገሩ እንኳን ገበያ ‹‹ሰው ከነ ክፋቱ ጥሩ ነው›› ይባል የለ፡፡
እኔን ግን እንዲህ ጤና ነስቶ ያብከነከነኝ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ ከአመት በፊት በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን (አተት) ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በቦታው ላይ የማስተካከያና የጽዳት እርምጃ ወስዶ ነበር። አስታውሳለሁ፤ በወቅቱ የተሰጠው መግለጫ ምክንያቱ ይከሰታል ተብሎ የተፈራው አተት ብቻ ሳይሆን፤ የአካባቢው ፅዳት በዘላቂነት መጠበቅ ስላለበት እንዲሁም በስፍራው ያለው የገበያ እንቅስቃሴ ለህጋዊ የንግድ ስርአት እንቅፋት በመሆኑ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የቦታውን ጥሩ ያልሆነ ታሪክ የማስወገድ ጅምር ነበር፡፡
ሃሳብ ያለ ተግባር ፍሬ ቢስ ነው እንጂ ሃሳቡስ ጥሩ ነበር፡፡ በእርግጥም አካባቢው መጥፎ ጠረን መለያው እስኪሆን የተበላሸ ሆኖ ከመኖሩ በላይ አይን ያወጣ ህገወጥ ንግድ የሚካሄ ድበትም ነበር። ምንም አይነት ግብር የማይከፍሉ የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች የህጋዊ ነጋዴዎችን ሱቅ በጀርባቸው አዝለውና መንገድ ዘግተው ቀን በቀን ትርፋቸውን ይሰበስቡበት ነበር። ይህ የመንገድ የግብይት ስርአት ተጠያቂና ሀላፊነት የሚወስድ ያልነበረበት፣ ሸማቹም ደረጃቸውና ምንጫቸው ያልታወቁ ምርቶችን እንዲገዙ የሚገደድበት፤ መንግስትም አረንጓዴ ተራራ የጫኑ ከሚመስሉት አይሱዙዎች ግብር ለመሰብሰብ ቋምጦ እንደተቁለጨለጨ የሚቀርቡት የገበያ ማእከል ነበር።
በወቅቱ የተወሰደው «የእርምትና የማጽዳት» ዘመቻ ይበል የሚያሰኝና ለህዝቡ እረፍት የሚሰጥ ጅምር ነበር።ምን ዋጋ አለው ገጣሚው ‹‹ደግ አይበረክትም›› እንዳለው ሁሉ አዲስ አበባም ጥሩ ጅምር አይቀጥልባትም፡፡ በዚህም ስራ ከተማ መስተዳድሩ ከወራቶች የዘለለ ምስጋናን መቸር አልቻለም፡፡ ቦታው ዛሬም እንደ ቀድሞው መለያውን የህገወጥ ንግድና የቆሻሻ መከማቻ የመሆን መብቱን አረጋግጧል። ለነገሩ ጽዳትን በተመለከተ በየመንደሩ አዲስ አበባን ‹‹ስም ብቻ›› የሚያሰኟት ቦታዎች ይበዙባት ይሆናል እንጂ አያንሷትም፡፡ እኛ ምናለብን ነገም ብንጠራ እንደ ከትላንት በስቲያው «የጋሽ አበራ ሞላ እንባ በከንቱ ፈሶ አይቀርም» እያልን መውጣታችን አይቀርም፡፡ በወረተኝነታችን በየአመቱ እየነቀልን ሳይሆን እየተከልን ስለምናደርቃቸው ችግኞችስ ምንስ ይሰማን ይሆን?። አቤት! ጨርሱ አይበሉን እንጂ ለመጀመር ማ ብሎን ፈርስት ነን።
እኔ 'ምለው ይሄ ወረተኝነት እስከ መቼ መለያችን እንደሆነ ይቀጥላል ? በቅርቡ በጠንካራ ሞራል በቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መሪነት ተጀምሮ የነበረውም የከተማ ጽዳት ዘመቻ ከወጣለት ሳምንታዊ ፕሮግራሙ ተፋትቶ በተመሳሳይ የወረተኝነቱ ሰለባ እየሆነ ከመጣ ሰነባብቷል፡፡ የከተማው ትራፊኮችም በአንድ ወቅት ጠጥተው የሚያሽከረክሩትን በትጋት ሲከታተሉ ነበር፡፡ አሁን ምን እንደነካቸው ባናውቅም ደብዛቸው ጠፍቷል። እኔ ግን ዝም ብዬ ሳስበው ጠጥቶ፤ ጠጥቶ የሚያሽከረክሩትን መቆጣጠር ክልክል ነው የሚል ህግ ወጥቶ ይመስለኛል፡፡ችግሩ ምንም ይሁን ምን ግን በኔትወርክ ሊሳበብ እንደሚችልም መጠራጠር የለብንም ። መቼም ዘንድሮ ኔትወርክ ምክንያት ያልሆነበት ችግር የለማ።
ለነገሩ የወረተኝነት ነገር በየመስኩ የሚታይ ነው። ወሬን ወሬ ያነሳዋል እንዲሉ መጻፌን ልቀጥል። ትልቅ ፋይዳ አላቸው ብለን ቀን እየቆረጥን ስለምናከብራቸው በአላትስ ምን ታዝበን ይሆን ?። አንድ ሁለቱን እንያቸው «የሰንደቅ አላማ ቀን» የሰንደቅ አላማ ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ በየአመቱ መከበር ከጀመረ አስረኛ አመቱን ይዟል። ታዲያ የዘንድሮም በአል በርካታ ቅድመ፣ ጊዜና ድህረ ኩነቶችን አሳልፏል። በአሉ ከመከበሩ ከቀናቶች በፊት እስከተከበረበት እለት ማግስት ሚዲያዎች ሰፊ ሽፋን ሰጥተው በርካታ ስራዎችን ለህዝብ አድርሰዋል። የሁሉም አይነት እቃ አዟሪና የመንገድ ላይ ነጋዴዎችም ከያዙት እቃ በተጓዳኝ በርከት ያሉና የተለያያ መጠን ያላቸውን ሰንደቅ ዓላማዎችን እያዞሩ ሲቸበችቡ ነበር። ኧረ! እንዴያውም አንዳንዶቹ ነጠላ የሚያክለውን ሰንደቅ አላማ በጀርባቸው አንግተው ሲዞሩም አይተናል።
በመሰረቱ የሰንደቅ አላማ መከበር የጀመረበት ምክንያት የሀገር ታላቅነት መገለጫ፤ የሕዝቦች የጋራና የአብሮነት ምሳሌ፣ የሰላምና የፍቅር የመቻቻልና መከባበር ብሎም የሕብርነትና የአንድነት መገለጫ በመሆኑ ነው፡፡ ስንጠቀልለው ደግሞ የብሔራዊ ፍቅር የብሔራዊ ማንነት መገለጫ አርማ በመሆኑ ነው። ድሮ በትምህርት ቤት ጠዋት ትምህርት ከመጀመራችን በፊት ተሰልፈን ባንዲራው ሲሰቀል ብሔራዊ መዝሙር መዘመር ግዴታቸው ነበር። ይሄ ማታም ከተሰቀለበት ሲወርድ ይደገማል።በነዚህ ጊዜያት በአካባቢው ማንም ሰው አይንቀሳቀስም ነበር፡፡ ሰንደቅ አላማ ክብሩ ከፍ ያለና የላቀ ስለሆነ፡፡
አሁን ግን ይሄ ሁሉ የለም።እንኳን ጠዋት የተሰቀለውን ማታ ለማውረድ ቀርቶ ለሰንደቅ አላማ ቀን የተወራውን እንደአመተ ንግስ 365 ቀን ቆጥሮ ካልሆነ የሚያስታውስ ያለ አይመስለኝም። ይሄን ስከትብላችሁ የምሰራበት ተቋም ሰንደቅ አላማ መስቀያ ትዝ አለችኝ፡፡ ብረቱ አፍ የለውም እንጂ ያችን የአንድ ቀን ሸብ ረብ አይቶ ጥምቀት የት ይከበራል ቢሉት በጥቅምት የመጀመሪያ ሰኞ እኔ ስር ባለ ነበር፡፡ሰሞኑን ደጋግሜ አየዋለሁ አንድም ቀን ሰንደቅ አላማውን ሲያወለበልብ አይቼው አላውቅም ። ትላንት ደግሞ ይሄንኑ እያሰብኩ አፈጠጥኩበት ለካ ማንጠልጠያ ገመዱንም ተነጥቆ ኖሯል። ታገስ አልኩ ቀኑ ይድረስ እንጂ ተንጠልጥለውም ቢሆን ማተቡን እንደሚያስሩ ለት በህሊናዬ እያሰብኩ። በእርግጥ እንደ ታፔላ ከወር ወር ተሰቅሎ የሚሰነብትባቸውም መንግስታዊ ድርጅቶች በርካታ ናቸው፡፡ ምናልባት ባልሳሳት ሰንደቅ አላማ አመት እስከ አመት ክብሩ የማይነፈገው በመከላከያ ሰራዊቱ ዘንድ ብቻ ይመስለኛል። ለነገሩ ይሄም ቢሆን አይደንቅም ሞልቶ ከተትረፈረፈ ተሽከርካሪ በሰሌዳቸው ላይ ሰንደቅ አላማዋን ለጥፈው የሚጓዙትስ እነሱ ብቻ አይደሉ።
ግን ማን ያውቃል ? አንድ ቀን እኛም ልቦና ይሰጠንና እንደካህኑ አስጀምሮ ላስፈጸምን... የምንልበት ቀን ይፈጠር ይሆናል።

 

ራስወርቅ ሙሉጌታ

Published in መዝናኛ

አይበገሬዎቹ ኢትዮጵያውያን አርበኞች በከፈሉት ድል ኢትዮጵያውያን አንገታችንን ቀና አድርገን ሄደናል። የዚህ ድል ባለቤቶችም እናት አርበኞች ጭምር ናቸውና ዝናቸው ተደጋግሞ ይነሳል። ስማቸው ከሚነሳው ዝናቸው ከሚነገርላቸው እናት አርበኛ መካከል እቴጌ ጣይቱ፣ ፊታውራሪ በላይነሽ ገብረአምላክ፣ ሸዋረገድ ገድሌ፣ ልዕልት ከበደች ስዩም ተጠቃሽ ናቸው። ለራበው አብልተው፤ ለጠማው ውሀ ሰጥተው፤ ቁስሉን አስረውና አይዞህ ብለው አበረታትተው ሀላፊነታቸውን ተወጥተዋል። ይሄ ስራቸውም በታሪክ የክብር መዝገብ ስማቸው እንዲሰፍር አድርጓል።
የእነእቴጌ ጣይቱ ጀግንነት፤ በኢጣሊያ ጦር ወረራ ጊዜ፣ በድሉም ወቅት የተናገሯቸው ንግግሮች፣ የሰሯቸው ስራዎች አሁን ላይ ስንሰማው አንዳች ስሜት ይፈጥራል። ‹‹እናቶቻችን ጀግኖች›› ናቸው ብለን እንድንኮራባቸው ያስገድዳል። እስኪ ያንን ዘመን መለስ ብለን እናስብ። እናቶቻችን አልተማሩም፤ እንደወንዶቹ አደባባይ የመውጣት እድሉ አልነበራቸውም። የፖለቲካውም ሆነ የኢኮኖሚ ተሳትፏቸው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ሀሳብ የመስጠት ዕድሉ የነበራቸው ጥቂቶች ነበሩ፡፡ ያም ሆኖ እናት አርበኞች የአገር ጉዳይ ሲነሳ፤ አገር በጠላት ጦር ተወረረ ሲባል «ሴቶች ነን» ብለው እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም። እኔም ለእናት አገሬ አለሁላት፤ መስራት የምችለውን እሰራለሁ ብለው «...ክተት ሰራዊት ጎስም ነጋሪት» ሲባል እነሱም ምላሽ ሰጥተዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሶስተኛ ዓመት የኢንጂነሪንግ ተማሪዋ እመቤት ሉሌም ታሪክ አስታውሳ የነገረችኝ ይህንኑ ነው። እመቤት የታሪክ ተማሪም ተመራማሪም አይደለችም። ሆኖም የአገሯን ታሪክ የምትናገረው መፃህፍትን አገላብጣ፣ የመገናኛ ብዙሀንን ተከታትላ፣ ቤተሰቦቿም ሆኑ ሌሎች ስለታሪክ ሲያወጉ ጆሮ ሰጥታ አዳምጣ ነው። እናም ስለታሪክ ማውራት ትወዳለች።
ታሪክን ማወቅና ያወቁትን ለሌላው በማሳወቅ የታሪክን ቀጣይነት ማረጋገጥ ጥሩ ቢሆንም እናት እና አባት አርበኞች ለኢትዮጵያ ነፃነት የከፈሉት መስዋዕትነት እና የተጎናፀፉትን ድል ብቻ በመዘከር መኩራራቱ አይጠቅመንም እና እኛስ ከእነሱ ምን መማር አለብን የሚለው ላይ አተኮርን።
እመቤት በዚህ ሀሳብ ትስማማለች። «ታሪክ ታሪክ ነው። በእርግጥም ታሪክ መታወቅ አለበት፡፡ ከኛም አልፎ አፍሪካን ያኮራ ታሪክ መዘንጋት አይኖርበትም። እኔም የምለው እኛም ይህንን ታሪክ የማስቀጠል አደራ አለብን ነው። ሁልጊዜ ጦርነት እንዲኖር ወራሪ እንዲመጣና እንድንመክት ማሰብና መጠበቅ አይኖርብንም። አሁን ሁሉም ነገር ተቀይሯል። ሴቶች ጭቆናን ድል ማድረግ የጀመሩበት ጊዜ ነው። መብታቸው ተከብሮ፣ ከወንዶች እኩል ተምረው፣ በፈለጉት የስራ ሙያ ተሰማርተው ራሳቸውን፣ ቤተሰብና አገራቸውንም መቀየር የቻሉበት ሰዓት ነው። ያም ሆኖ ግን አሁንም ያለው ነገር ፍፁምና ምቹ አይደለም» ትላለች።
የፖለቲካ አመራሩ አሁንም ብዙሃኑ ወንዶች ናቸው። በከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ ያለው የወንዱ ቁጥር ከሴቶች በስንት እጅ እንደሚበልጥ ማየት ይቻላል። ሌላ ጥናት ማድረግ ሳያስፈልግ ይህንን በማየት ብቻ ሴቶች ገና ናቸው ማለት ይቻላል። በራሳችንም ሆነ በህብረተሰቡ ጫናና አመለካከት ምክንያት መውጣት አልቻልንም፡፡ የባህል ተፅዕኖው ከተፈጥሮ ጋር ተዳምሮ ወደኋላ እየጎተተን መሆኑም የሚካድ አይደለም ትላለች። ለውጦች፣ መሻሻሎች እንዳሉ ሁሉ አሁንም ችግሮች አሉ የሚለው እምነቷ የጎላ ነው።
እመቤት የአመለካከት ችግሩ ከሁሉም በላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል ባይ ናት። ስለዚህ ሴቶችም ራሳቸውን በሁሉም ዘርፍ ለማውጣት ጥረት ማድረግ፤ ወንዶችም ሴቶች እድሉን ካገኙ በተሻለ ደረጃ፣ በታማኝነትና በብቃት ይሰራሉ ብለው ማሰብ አለባቸው ትላለች። ለዚህም የሴቶችን ዝግጁነት ይጠይቃል። ይሄ ሲሆን የዛሬ 77 ዓመት ስለምናነሳቸው ጀግኖች አርበኞች ብቻ ሳይሆን ዛሬ ስላለችው ጀግኒት ሴት ማንሳት እንጀምራልን። ያኔ ጀግንነቱ በየአቅጣጫው ይሆናል ትላለች።
የየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ነዋሪና በግል ስራ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ ህይወት በቀለ «ይሄ ትውልድ ታሪክ ሰሚ ብቻ ሳይሆን ታሪክ ሰሪ መሆን አለበት» የሚል እምነት አላቸው። ‹‹በተለይ ሴቶች አሁንም ብዙ ነገሮች ያሸንፉናል። የሚፈታተን ነገር ሲያጋጥመን እንዴት አድርገን ድል ማድረግ እንዳለብን ከማሰብ፣ ያጋጠመንን ነገር ለማሸነፍ ከመልፋት ይልቅ ተስፋ መቁረጥ ጎልቶ ይታያል። ያኔ እናት አርበኞች ስንቅ ተሸክመው አይዞህ እያሉ ሲከተሉ ‹ድሉ የእኛ ነው› ከሚል ቆራጥነት ተነስተው ነው። እኛ ዘመናዊ መሳሪያ የለን፤ ጥይት የለን ቢሉ ኖሮ ለዛሬው ታሪክ ማክበር የሚበቃ ሥራ አይሰሩም ነበር። እነሱ ግን ያለንን ይዘን አምላክ ይረዳናል ብለው በሙሉ እምነትና ወኔ በመዝመታቸው፣ የወደቀውን የተጎዳውን ሲያዩ፣ የጊዜውን መርዘም ሲቆጥሩ ተስፋ አልቆረጡም›› ይላሉ፡፡
ወይዘሮ ህይወት እንደሚሉት፤ ሴቶች ከእነዛ አርበኞች ብዙ መማር አለባቸው። ትልቁ ነገር አንድን ጉዳይ በድል እወጣዋለሁ ብሎ ማሰብ ነው። አስቦ በቆራጥነት መታገል ይገባል። አንድ ነገር ሲታሰብ ብዙ መሰናክሎች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ አስቀድሞ ማሰብ ያስፈልጋል። በአጠቃላይ ግን ተስፋ አለመቁረጥ ለውጤት ያበቃል ይላሉ።
ወጣት መዓዛ ለይኩን በጥቃቅንና አነስተኛ በምግብ ዝግጅት ስራ ላይ ተሰማርታለች። ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ከሰባት ጓደኞቿ ጋር በመደራጀት ከራሳቸው ገንዘብ በማዋጣት ለሀዘን ቤት፣ ለግብዧ እንዲሁም ለልደት ምግብ በትዕዛዝ በማዘጋጀት የስራ ዕድል ፈጥራ ውጤታማ መሆን መቻሏን ትናገራለች። በተለምዶ «አርከበ ሱቅ» የሚባለውን የስራ ቦታ በመከራየት ገርጂ አካባቢ እየሰራች ትገኛለች።
ወጣቷ እንደምትለው፤ ይሄ ትውልድ የውጪ ወራሪ አያሳስበውም። ወራሪ እንኳን ቢመጣ የተደራጀና የሰለጠነ የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ ዘመናዊ መሳሪያ አለ። በእርግጥ አገር ስትነካ ወንድ፣ ሴት፣ ወጣት፣ ወታደር ላይባል ይችላል። ሆኖም ግን ሁሉንም ማድረግ የሚያስችል ሁኔታ አለ። ስለዚህ እንደ ቀደሙት ሴቶች መሆን አይጠበቅም። የአሁኑ የሴቶች ትኩረት ራስን እና አገርን በማሳደግ በአገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ ለውጥ ማስመዝገብ ነው፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ሴቶች የኢኮኖሚ ጥገኛ ከመሆን እየተላቀቁ ነው። በራሳቸው ይሰራሉ፤ ኢኮኖሚያቸው የሚያድግበትን ተጨማሪ ገቢ የሚያገኙበትን ስራ ይፈጥራሉ። ሌላው ቀርቶ የቤት እመቤት የሆኑ ሴቶች በቤታቸው የባልትና ውጤቶችን በማዘጋጀት፣ ሽንኩርት በመክተፍ፣ በርበሬ በመደለዝ፣ ድፎ ዳቦ በመጋገር... ለራሳቸው የገንዘብ ምንጭ እየፈጠሩ ናቸው። ይሄ የሚያሳየው የአስተሳሰብ ለውጥ መምጣቱን ነው፤ በራስ መተማመን መፈጠሩን ያመላክታል።
ይሄ ሴቶች ላመኑበት ጉዳይ ቆራጥ ከሆኑ ምንም ነገር እንደማያቅታቸው ያሳያል። አርበኛ እናቶች ያስተማሩት አይበገሬነትን ነው። ዘዴኛ መሆንን፣ በብልሀት ብዙ ነገሮችን ማሸነፍ እንደሚቻል አሳውቀዋል። የዘመኑ ሴት ደግሞ የእነሱን ታሪክ መዘመር ብቻ ሳይሆን ታሪክ ሰሪ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ሴት በሁሉም መስክ አቅም መሆኗን ሰርተው ተለውጠው፤ አገራቸውንም ለውጠን ማሳየት ይኖርባቸዋል። አሁን ሴቶች «አይደፍሩትም» በሚባሉ ስራዎች ላይ ተሰማርተው ስማቸው ከፍ ብሎ ሲጠራ፤ የስራቸው ውጤት ሲገለጽ እየታየ ነው። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀን ማንሳት እንችላለን። ሌሎችም ብዙ ውጤታማ ሴቶች መብቀል ችለዋል። ከዚህም በላይ በመስራት በታሪክ መዝገብ ለመመዝገብ ቆራጥ ሆኖ መንቀሳቀስ አስፈላጊ መሆኑን ትገልፃለች።
በእርግጥም ጊዜው በአይበገሬነት ስሜት ጦር ሜዳ የሚዘመትበት አይደለም፡፡ ወቅቱ ከድህነት ጋር ጦርነት የሚካሄድበት ነው፡፡ ጦርነቱ በዛው ባለንበት ቦታ የሚካሄድ ነው፡፡ ጉዞ ለመጓዝ ስንቅ ማዘጋጀትና ለነገ ማለትን አይጠብቅም፡፡ የሚጠይቀው ዛሬውኑ ተነስቶ ባሉበት ቦታ ድህነትን መዋጋት ብቻ ነው፡፡ አሁን ድህነትን ታሪክ የሚያደርጉ እና በክብር መዝገብ ላይ የሚሰፍሩ ሴቶች ይፈለጋሉ፡፡ ለዚህም ጊዜው የሚጠይቀውን ሆነንና ሰርተን በታሪክ መዝገብ እንስፈር፤ ከአይበገሬዎቹ እናት አርበኞች ታሪክ ጀርባ ያለው ሚስጢርም ይሄው ነው። የተማርነውን እንተግብር!

አልማዝ አያሌው

Published in ማህበራዊ

 

የአርበኞች በዓል የነጻነት ተምሳሌት፣ እናትና አባት አርበኞች የከፈሉት የመስዋዕትነት ውጤት ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን የጋራ ድል ቀን፡፡ በዓሉ ሲነሳም ኢትዮጵያውያን የአሸናፊነት፣ የአልበገር ባይነትና የነጻነት ተምሳሌት የጋራ አኩሪ ታሪካቸው ተደርጎ ይታያል፡፡
ዛሬ እየተከበረ እንዳለው የአርበኞች መታሰቢያ ባሉ በዓላት ኢትዮጵያውያንን የጋራ የሚያደርጉ በዓላት አሉ፡፡ በዓላቱን ዜጎች በጋራና ባንድነት በደመቀ ሁኔታ ሊያከብሩት የሚገባ እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ ይሁን እንጂ ባለፉት 26 ዓመታት የጋራ በዓላት ተገቢ ትኩረት ተሰጥቷቸው በደመቀ፣ በጋራ ስሜት ተከብረዋል ለማለት አያስደፍርም የሚሉ አልታጡም፡፡
የጋራ ከሚባሉት በዓላት መካከል የካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ፣ የካቲት 23 የአደዋ ድል መታሰቢያ፣ ሚያዝያ 27 የአርበኞች መታሰቢያ ፣ የሰንደቅ ዓላማ ቀንና የመከላከያ ቀንን ለአብነት መውሰድ ይቻላል፡፡
አንዳንድ በዓላት መከበር የጀመሩት በቅርብ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ከዕለት የዜና ሽፋን በዘለለ በውይይትና በተለያዩ መርሃ ግብሮች ሲከበሩ አይታይም፡፡ አንዳንድ በአላቶችን በማክበር አሁን ጥሩ ጅምር ቢኖርም፤ በጥቅል ሲታይ ግን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ለሚያስብሉ የጋራ በዓላትና ታሪኮች ተገቢ ትኩረት አለመደረጉን መታዘብ ይቻላል፡፡
የጋራ በዓላት ትልቁ ዓላማቸው ኢትዮጵያዊነት ስሜትን ማጠናከር እና ማደስ እንዲሁም ዜጎች በኢትዮጵያዊነታቸው እንዲኮሩ ማስቻል ነው፡፡ ታሪክን የማሳወቅ አቅማቸው ጠንካራ ነው፡፡ እነዚህ በዓላት ትኩረት ካላገኙ ኢትዮጵያዊነት ስሜት እየተዳከመ እንዲሄድ፣ አንድነትም እንዲላላ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባል፡፡
በአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ የሰብአዊ መብትና የፌዴራሊዝም መምህር ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ ያሉት ይህንኑ ነው። የጋራ በዓላት የየራሳቸው ትርጉም እንዳላቸው ያነሳሉ፡፡ ለምሳሌ በየዓመቱ ሚያዝያ 27 ቀን የሚከበረው የአርበኞች መታሰቢያ በዓል፤ የድል በዓል መሆኑን፣ ጣሊያን ኢትዮጵያን ወርሮ በነበረበት ወቅት ኢትዮጵያውያን በከፈሉት መስዋዕትነት ነጻነት የተረጋገጠበት ዕለት መሆኑንም ይናገራሉ፡፡
እርሳቸው እንደሚያብራሩት፤ ዕለቱ የተወሰነ ቡድን ብቻ የሚያከብረው በዓል አይደለም፡፡ የሁሉም የአገሪቱ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ድል ነው፡፡ ስለዚህ በጋራ ሊከበር ይገባል፡፡ የአርበኞች በዓል የነጻነት ተምሳሌት ነው፡፡ ቅድመ አያቶች የከፈሉት የመስዋዕትነት ውጤት ነው፡፡ በዓሉ ሲከበር በተወሰነ አካባቢ ብቻ የሚከበር መሆን የለበትም፡፡ በጦርነቱ በቀጥታ በተሳተፉ በሚታወቁ አርበኞች ብቻም ሊሆን አይችልም፡፡ በዓሉ የጋራ ታሪክ አካልና የማንነት መገለጫም ጭምር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ስትነሳ የአሸናፊነት፣ የአልበገር ባይነትና የነጻነት ተምሳሌት የጋራ አኩሪ ታሪክ ተደርጎ መታየት አለበት ይላሉ፡፡
የአደዋ በዓልም ተመሳሳይ ነው፡፡ ለአለም ጥቁር ህዝቦች ትልቅ የነጻነት ጮራ ፈንጣቂ ተደርጎ ይታያል፡፡ ትልቅ ድል የተገኘበት ቀንም በመሆኑ የዚህኛው የዛኛው ሳይባል በጋራ ማክበር ተገቢ መሆኑን ይመክራሉ፡፡ ሌሎችም የጋራ የሚሆኑ ሃብቶች የታሪክ፣ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ቅርሶች አሉ፡፡ እነዚህን ሁሉም ሰው የእኛ ናቸው ብሎ ሊንከባከባቸው ይገባል ይላሉ ዶክተር ሲሳይ፡፡
ባለፉት 26 ዓመታት የጋራ በዓላት ተገቢ ቦታ ተሰጥቷቸው በደመቀ፣ የጋራ ስሜት ባለው መልኩ ተከብረዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ለእዚህ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ ለብሄር ብሄረሰቦች ማንነት ትልቅ ቦታ ሰጥቷል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የክልሎችና የፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት ብሄረሰባዊ መልክ ያለው ስለሆነ ሁሉም ወደ የራሱ የማየት ነገር ነበረ፡፡ ለራሱ ማንነት፣ ለራሱ መገለጫዎች እና ለራሱ በዓላት ቅድሚያ ሰጥቷል። ለምሳሌ አንዳንዶቹን ለአብነት ብንመለከት ጥሩ ነው፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች በዓል ሲታይ የህወሃትን በዓል ለማክበር የትግራይ ቴሌቪዥን ለወራት በጉዳዩ ዙሪያ ሲዘክር ይታያል፣ የብአዴን በዓል ለማክበር የአማራ መገናኛ ብዙሃን ለወር ወይም ለሳምንታት ሽፋን ሰጥቶ ሲዘግብ ይታያል፣ ኦሮሚያ የኦህዴድ በዓልን ፣የደቡብ መገናኛ ብዙሃን የደኢህዴንን ሌሎቹም ተመሳሳይ ሁኔታ ይታይባቸዋል፡፡
ከዚህ አልፎም ለራስ ቋንቋና ባህል ትልቅ ቦታ የመሰጠት ነገር አለ፡፡ ይሄ ጥሩ ቢሆንም ሚዛኑን መጠበቅ ግን ይኖርበታል፡፡ ሌላው ቀርቶ ኢህአዴግ የራሱ በዓሎች ከሆኑት አንዱ የግንቦት 20 በዓልን ባግባቡ እያከበረው ነወይ? ብሎ ማየት ተገቢ ነው፡፡ ባግባቡ ሲከበር አይታይም፡፡ እንዲሁ በተለያየ መልኩ አንዳንድ መስሪያ ቤቶች ዕለቱን በውይይትና በተመሳሳይ ሁኔታ ሲያከብሩት ይታያል፡፡ ስለዚህ በጋራ ኢትዮጵያዊ ለሚያስብሉ ወይም የጋራ ለሆኑ በዓል እና ታሪክ ተገቢ ትኩረት ያለመስጠት አንዱ ማሳያ ተደርጎ ሊታይ ይችላል፡፡
ሌላው ቀርቶ የታሪክ ትምህርት ለትውልዱ እየተሰጠ አይደለም፡፡ ይሄ አንዱ የጋራ ማንነት መገለጫ ታሪካችን ነው፡፡ ነገር ግን የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች 11ኛ እና 12 ኛ ክፍል ላይ ጭራሽ ታሪክ አይማሩም፡፡ የህብረተሰብ ትምህርት ተማሪዎች 11ኛ እና 12 ኛ ክፍል የተወሰነ ታሪክ ይማራሉ። ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በኋላ ደግሞ የኢትዮጵያን ታሪክ የጋራ ማንነትን በሚያንጸባርቅ ሁኔታ ትምህርት አይሰጥም፡፡ ይህ በራሱ እንዲጎድል ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ ሚዛኑን እንዲጠብቅ ማድረግ ይገባል፡፡ የብሄር፣ ብሄረሰቦችን በዓል፣ ቋንቋ፣ ማንነት፣ የዘመን መለወጫ እና የተለያዩ መገለጫዎች በተገቢው መልኩ ሊከበሩ ይገባል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ የጋራ የሚያደርጉ በዓላትን ደግሞ በተገቢው መልኩ መከበር ይኖርባቸዋል፡፡ የሰንደቅ ዓላማ ቀን እንኳን መከበር የጀመረው ዘግይቶ ነው፡፡ ይህ በዓልም ከዕለቱ የዜና ሽፋን በዘለለ እንደሌሎቹ በውይይትና በተለያዩ መርሃ ግብሮች ሲከበር አይታይም፡፡ የመከላከያ ቀን አንዱ የጋራ መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በአሉን በማክበር አሁን ጥሩ ጅምር ይታያል፡፡ በዝርዝር ሲታይ ግን በአብዛኛው ሲያመዝን የነበረው ለብሄር፣ ብሄረሰብ ማንነት አልያም ወደ አካባቢያዊነት የማተኮር ሁኔታ ነው። ስለዚህ አገራዊ ማንነቶች ላይ ተገቢ ትኩረት አልተደረገም፡፡
ሁሉም ወደራሱ ሲያተኩር የጋራ የሚያደርገውን ትልቁን ስዕል ባግባቡ እንዳይመለከት ያደርገዋል፡፡ የጋራ በዓላት ትልቁ ዓላማቸው ኢትዮጵያዊነት ስሜትን ማጠናከርና ማደስ እንዲሁም ዜጎች በኢትዮጵያዊነታቸው እንዲኮሩ ማስቻል ነው፡፡ የጋራ በዓላት ትኩረት አለማግኘታቸው ኢትዮጵያዊነት ስሜት እየተዳከመ እንዲሄድ አንድነትም እንዲላላ ያደርጋል፡፡ በአንድ አገር ላይ በጋራ የሚያግባባ ቋንቋ ሊኖር ሲገባ አሁን የጋራ የሚያደርግ ቋንቋ አለ ማለት አይቻልም፡፡
ስለዚህ ሊያግባቡ የሚችሉ የጋራ ቋንቋዎች ሊኖሩ ይገባል፡፡ በዚህ ላይ የሌሎች አገሮች ተሞክሮን መውሰድ ይቻላል፡፡ ስዊዘርላንድ የጋራ አገራዊ ቋንቋ ሶስት ሆኖ እንዲያገለግል አድርገዋል፡፡ ካናዳ አንድ ብቻ ኪዩቤክ የሚባል ፈረንሳይኛ ተናጋሪ አገር አላት፡፡ ለፈረንሳይኛ ተናጋሪው ፈረንሳይኛ ከእንግሊዝኛ ቀጥሎ የጋራ ቋንቋ ሆኖ ያገለግላል ፡፡
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ80 በላይ ብሄር ብሄረሰብ አለ፡፡ የተለያየ ቋንቋ አለ እየተባለ እንኳን በጣም በርካታ ህዝብ የሚናገራቸውን ቋንቋዎች የአገሪቱ ቋንቋ ሆኖ እንዲነገር አልተደረገም፡፡ አማርኛን እንኳን የፌዴራል መንግስት የስራ ቋንቋ እንጂ በመላ አገሪቱ ሊሰራበት፣ ትምህርት ሊሰጥበት በሚችል መልኩ ብሄራዊ ቋንቋ አልሆነም፡፡ በዚህ መልክ ሲታይ አማርኛን በአግባቡ እየተጠቀምንበት አይደለም፡፡ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች አንዳንድ ጊዜ ወይ አማርኛን አሊያም እንግሊዝኛን በአግባቡ ባለማወቃቸው ትምህርት ለመስጠት ከባድ ሆኖ ይታያል፡፡ በመሆኑም የጋራ ቋንቋ ሊኖር ይገባል፣ የጋራ መገለጫዎችም ባግባቡ ሊከበሩ ይገባሉ፡፡ ይህ ሲሆን ኢትዮጵያዊነት እያደገና እየጠነከረ ይሄዳል፡፡
ዶክተር ሲሳይ፤ የድሮ ተማሪዎች አገራዊ አጀንዳ በማንሳት ወይ የዩኒቨርሲቲውን አስተዳደር አሊያም መንግስትን ይቃወሙ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ አሁን ይህ ሁኔታ ተቀይሮ አዲስ ገጽታ እንደሚስተዋል ያነሳሉ፡፡ ህዝቦች እርስ በእርስ ሲወቃቀሱና አንዳንዴም ሲደባደቡ በገሃድ እንደሚታይ ማስተዋላቸውን ይጠቁማሉ፡፡ ይህ በአገሪቱ ታሪክ ታይቶ አይታወቅም፣ በአንድነት ለመኖርም አደጋ እንደመሆኑ መቅረት እንደሚገባውም ይገልጻሉ፡፡
ዶክተር ሲሳይ እንደሚገልጹት፤ መንግስት ለልዩነት ትኩረት መስጠቱ እስካሁን ለተፈጠረው ችግር ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህን ለልዩነት የተሰጠውን ትኩረት መመለስ ይገባል፡፡ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሰየሙ በኋላ በየክልሉ በመሄድ ኢትዮጵያዊነትን የሚያስገነዝብ ስራ እየሰሩ ናቸው፡፡ ይህ የሚበረታታ ነው፡፡ ግን በእርሳቸው ብቻ ታጥሮ መቅረት የለበትም፡፡ ሁሉም የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች አገራዊ ፋይዳ ላላቸው በዓላት ትኩረት ሊሰጡ ይገባል፡፡
ለዚህ በተለይም የባህልና ቱሪዝም እና የትምህርት ሚኒስቴሮች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው የሚሉት ዶክተር ሲሳይ፤ ትኩረት ሰጥተው መስራት ይኖርባቸዋልም ይላሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያዊነትን አጉልቶ በማሳየት፣ የጋራ ባህል በማሳደግ፣ ቋንቋ በደንብ ተጠናክሮ አገልግሎት መስጠት እንዲችል የጋራ ታሪክ በጠራ መልኩ እንዲዘጋጅ እንዲሁም በስርዓተ ትምህርት እንዲካተት በማድረግ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ብለዋል፡፡
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ የተማረው ክፍል በማስተማርና በማሰልጠን የራሳቸውን ድርሻ መወጣት ይገባቸዋል ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህገ መንግስት አስተምህሮ በማስፋፋት፣ ትውልዱ መልካም ስነ ምግባር እንዲይዝ በማድረግ አገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ትላልቅ ኩነቶችን አጉልቶ በማሳየት ከፍተኛውን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባውም ያመለክታሉ፡፡
መገናኛ ብዙሃን ትልቅ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ አሁን አሁን የመንግስት ዝንባሌ ወደ ኢትዮጵያዊነት ሲመጣ ሚዲያዎች እየሰሩ ናቸው፡፡ ይህ ቀደም ብሎ መጀመር ነበረበት፡፡ መገናኛ ብዙሃን የባለስልጣናትን ይሁንታ እያዩ የሚሄዱ መሆን የለባቸውም፡፡ ሚዲያ በሌላ አገር አራተኛው የመንግስት አካል ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ትልቅ ተጽእኖ ስለሚፈጥርና ፋይዳውም ትልቅ መሆኑ ስለሚታመን ነው፡፡ በእኛ አገር ግን ይህንን ቦታ ይዞ አናገኘውም፡፡ ሚዲያ ራሱ አጀንዳ ቀርጾ የሚሰራ መሆን አለበት፡፡ መንግስትን ጨምሮ ሌሎች አካላትም በእዛ አጀንዳ ዙሪያ ትኩረት እንዲኖራቸው ሊያደርግ ይገባል፡፡ ይህንን ማስወገድ ከተቻለ እርግጠኛ ነኝ ውጤት ሊመጣ ይችላል ብዬ አስባለሁ ሲሉም ዶክተር ሲሳይ ይገልጻሉ፡፡
በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህሩ አቶ ሲሳይ ተወልደመድህን፤ የጋራ በዓላት አገራዊ ፋይዳቸው እጅግ ብዙ ነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡ የበዓሉ ባለቤቶች ሲያከብሩት ታሪኩን በማስታወስ ለአሁን ጊዜ ትልቅ አንድምታ አለው ባይ ናቸው፡፡ እንደ አድዋ እና የአርበኞች በዓል አባቶች ያደረጉት ተጋድሎ የሚዘከርበት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በመሆኑም እጅግ ከፍተኛ በሆነ መነሳሳት የአገሪቱ ህዝቦች እንዲስማሙ ወይም በጋራ እንዲሆኑ የሚያደርጉ መሆናቸውን ነው የሚናገሩት፡፡
መምህር ሲሳይ ወጣቱ ትውልድ የአባቶቹን ተጋድሎ የሚዘክርበት ዕለት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ከእነርሱ ተምሮ አሁን ባለው ጊዜ በተሻለ ሁኔታ የራሱን ድርሻ ወስዶ እንዲሰራ የሚነሳሳበት እንደሆነም ያክላሉ፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ሲታይ ግን በዓሎቹ ላይ በደንብ እንዳልተሰ ራባቸው ያመለክታል ባይ ናቸው፡፡ ከምክንያቶቹ አንዱ ነው ብለው የሚጠቅሱትም አብዛኛው ጊዜ በዓሎቹ ለህዝብ ጆሮ የሚደርሱት የበዓሉ ቀን ሲደርስ ከሁለት ቀን ባልዘለለ ጊዜ መሆኑንና ትውልዱ ስለበዓላቱ ጥልቅ ግንዛቤ አለመያዙን ነው፡፡
የበዓሉ ምንነት ለትውልድ ያን ያክል አልተላለፈም የሚሉት መምህር ሲሳይ፤ ለአዲሱ ትውልድ መልዕክት መተላለፍ የሚገባው በምን መልኩ ስለመሆኑ መታየት ይኖርበታል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ አጠቃላይ ያከባበሩ ሁኔታ፣ ለምን እንደሚከበር፣ መከበር የጀመረበት ጊዜ ዝርዝር ሁኔታ በማየት በቀጣይ በስፋት ቢሰራበት መልካም ነው ሲሉም ይመክራሉ፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከበሩ ብዙ በዓላት አሉ፡፡ እየተከበሩ ያሉትን ስንመለከትም በፓርቲ ውስጥ ያሉ በዓላት ናቸው፡፡ ብዙ ሃብት የሚፈስሰው፣ ብዙ የሚሰራበትም ለእነዚህ በዓላት ነው፡፡ አገራዊ በዓላት አከባበርን ስንመለከት በመገናኛ ብዙሃን ሽፋን በማግኘት፣ በዝግጅት፣ በበጀትም በጣም ያነሰ ሆነው ነው የሚታዩት፡፡ እነዚህን አገራዊ አንድነትና መግባባት ሊያመጡ የሚችሉ በዓላት ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቶባቸው በስፋት ሊከበሩ ይገባቸዋል ይላሉ፡፡
አንዳንድ በዓሎችን ወጣቱ ትውልድ በደንብ የሚያውቃቸው አይመስለኝም የሚሉት መምህር ሲሳይ፤ በዕለቱ በመገናኛ ብዙሃን ስለ በዓሉ የሚነገረው ብቻውን በቂ አይደለም ሲሉ ይጠቁማሉ፡፡ በመሆኑም በደንብ መሰራት አለበት ባይ ናቸው፡፡ በቀጣይ ትኩረት የማይሰጣቸው ከሆነ የሚቀጥለው ትውልድ ሙሉ ለሙሉ ላያውቃቸው ይችላል ወይም ከቀን መቁጠሪያም ሊጠፉ ይችላሉ የሚል ስጋትም አድሮባቸዋል፡፡ በመሆኑም ብዙ ባለድርሻዎች ያገባናል የሚሉ ሁሉ ተሳትፎ ቢያደርጉ እና በዓሉ በደንብ እውቅና ተሰጥቶት ቢከበር ትውልዱም እየተቀባበለ ሊያከብረው ይችላል፡፡ አለበለዛ ግን ሊዘነጉና ሊጠፉ ይችላሉ፣ አገራዊ አንድነትንም የማስተሳሰር አቅማቸው በጣም ያነሰ ይሆናል፡፡
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አምባሳደር አለማየሁ አበበ፤ የአርበኞች ማህበር በ1931 ዓ.ም መቋቋሙን ያስታውሱና፤ አርበኞች በየአካባቢው በቡድን ሆነው ጠላትን ሲመክቱ በነበረበት ወቅት በተጠናከረ መልኩ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ማገዝ ዋና አላማው መሆኑን ይናገራሉ። በወቅቱ እንቅስቃሴው ጠንካራ ስላልነበረ፣ የመገናኛ ብዙሃን በደንብ ባለመደራጀቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ አርበኞችን በሙሉ ማግኘት አለመቻሉንም ያክላሉ፡፡
ከ1933 ዓ.ም ከተገኘው ድል በኋላ ማህበሩ ከመንግስት ዕውቅና ወስዶ መንቀሳቀስ መቀጠሉንም ነው የሚገልጹት፡፡ በየዓመቱ መስዋዕት የከፈሉ አርበኞችን እንዘክራለን፡፡ የካቲት 12 የደረሰውን ግፍ የምናስታውሰውና ለወደፊቱም ወጣቱ ትውልድ አባቶቹ ያደረጉትን መስዋዕትነት መሰረት አድርጎ አገሩን እንዲወድ፣ ታማኝ እንዲሆንና ዘብ እንዲቆም ግፊት ለማድረግም የበዓሉ መከበር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አምባሳደር አለማየሁ ይናገራሉ፡፡
እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ ቤተሰብ ልጆቹን ማነጽ ይኖርበታል፣ ትምህርት ሚኒስቴር በስርዓተ ትምህርት ተካትቶ ትውልዱ ታሪኩን እንዲያውቅና መልካም ስነምግባር ይዞ እንዲታነጽ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በየዓመቱ አርበኞችን የሚዘክር በዓል እየተከበረ ያለበት ሁኔታ በቂ አይደለም፡፡ በዓሉ እየተከበረ ካለበት ሁኔታ በላይ በደመቀ መልኩ ሊከበር ይገባዋል፡፡ ህዝቡን የሚቀሰቅስ ነገር ሊደረግ ይገባል፣ ሄሊኮፕተር በዓሉ በሚከበርበት ስፍራ አንጃብቦ ቀስቃሽ ጽሁፎችን በትኖ ልዩ ስሜት ቢፈጠር ምኞታችን ነው፡፡ አንድ ብርጌድ ጦር ተሰልፎ እንዲከበር ፍላጎት አለን፡፡ ጊዜው ሲፈቅድ እንዲህ በደመቀ መልኩ ይከበራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ደምቆ መከበሩ የወጣቱን ስሜት በመቀስቀስ የበለጠ ታሪኩን እንዲገነዘብ ለማድረግ ያግዛል፡፡
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር የምስራቅ ጎጃም ሊቀመንበር ሊቀ ማዕምራን ፈንታሁን አለሙ፤ ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ህዝብ የአገር ፍቅር እንደነበረው ያስታውሱና ጠላት አገሪቱን መውረሩን ተከትሎም ንጉሰ ነገስቱ አዋጅ ሲያውጁ ‹‹ክተት ሰራዊት ምታ ነጋሪት›› ሲባል አንዱ ከሌላው ሳይለይ በጠቅላላ ስንቅ ተሸክሞ በዱር በገደል ንብረቱንና ልጁን ትቶ ነጻነቱን ለማረጋገጥ ይወጣ እንደነበረም ነው የሚያብራሩት፡፡
ቀደም ሲል በቤተ ክርስቲያንም ፈጣሪ ኢትዮጵያን እንዲጠብቅ ጸሎት ይደረግ እንደነበረ የሚያስታውሱት ሊቀ ማዕምራን ፈንታሁን፤ የአሁኑ ትውልድ ይህ በአንድነት ሊከበር የሚገባውን በዓልና የኢትዮጵያ አንድነትና ማንነት የሚያደምቁ በዓላት ባግባቡ አይታወቁም ሲሉ ያመለክታሉ፡፡ በዓላቱ ትኩረት ተሰጥቷቸው በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ግንዛቤ እንዲፈጠርባቸው መደረግ እንደሚኖርበትም ይገልጻሉ፡፡
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር የምክር ቤት አባል አቶ ጌታቸው ወረደ ጌታሁን ዛሬ የነጻነት ቀን መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ በዓሉ አባቶችና እናቶች አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍስሰው ነጻ ያደረጉበት ዕለት መሆኑን በማሰብ እንደሚከበርም ነው የሚናገሩት፡፡
የካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ፣ የካቲት 23 የአደዋ ድል መታሰቢያ፣ እና ሚያዝያ 27 የአርበኞች መታሰቢያ በዓልን በዓመት ሶስት ቀናት ይከበራሉ ሲሉ ያስታውሳሉ፡፡ ከነዚህ በዓላትም ሁለቱን መንግስት በቀን መቁጠሪያ አካትቶ ዝግ እንዲሆን መወሰኑን በመጥቀስም፤ በመንግስት በኩል መደረግ የሚገባው መሟላቱን ይናገራሉ፡፡ ‹‹የቀረ ነው ብዬ በቅሬታ የማነሳው የመገናኛ ብዙሃን ስለበዓላቱ አከባበር የሚሰጠው ሽፋን አነስተኛ መሆኑን ነው›› ሲሉም ይጠቁማሉ፡፡
ወጣቶች ዝግ የሆነበትና በዓላቱ የሚከበሩት ምክንያት ምንን ለማስታወስ እንደሆነ ባግባቡ አይገነዘቡም፡፡ ለዚህም የትምህርት ተቋማት በስርዓተ ትምህርት አካትተው ሊያስተምሩና ግንዛቤ የማስፋት ስራን ሊሰሩ ይገባል ይላሉ፡፡
አቶ ጌታቸው በእነርሱ እድሜ ትምህርት ቤት ግቢ ተሰልፈው ወደ ክፍላቸው ከመግባታቸው አስቀድመው ‹‹ሰላም ላጽማችሁ፣ አርበኞች በዱር በገደል ለቀራችሁ፣ መኖሪያ ሳታጡ ቤት ሳይቸግራችሁ፣ የአገርን መዋረድ አናይም ብላችሁ›› ብለው ይዘክሩ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ የአሁኑ ትውልድ የአርበኞችን ተጋድሎ የሚያውቅበት መድረክ ባለመኖሩ ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት አለበት ባይ ናቸው፡፡
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር የምክር ቤት አባል ኮሎኔል አንዳርጌ ደስታ እንደሚሉት፤ አዲሱ ትውልድ አባቶቹና አያቶቹ የከፈሉትን መስዋዕትነት ማደስ ይገባዋል፡፡ አሁን ያለው ትውልድ በነጻነት እንዲኖር አርበኞች የከፈሉት መስዋዕትነት ሊዘነጋ አይገባውም፡፡ ለአገር ነጻነት እና አንድነት ቤት ንብረታቸውን ጥለው በረሃ ገብተው ከፍተኛ የሆነና ለአለም ምሳሌ የሚሆን መስዋዕት ከፍለዋል፡፡ በከፈሉት መስዋዕትም ለአገራቸው ነጻነትን አስገኝተዋል፡፡
አዲሱ ትውልድ ከዚህ ብዙ መማር ይችላል፡፡ ይህንንም ካላደሰው የተደከመው ሁሉ ዋጋ ያጣል፡፡ በመሆኑም ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ ይህ ትውልድ በነጻነት የመማር፣ የመኖር ዕድል ያገኘው አያቶቹ እና አባቶቹ በከፈሉት መስዋዕትነት መሆኑን መገንዘብና መረዳት ይገባዋል፡፡ በዚህ መረዳት ከፍተኛ የአገር ፍቅር እና አንድነት ሊኖረው ይገባል፡፡ በጋራ ሆኖ የማክበር ሁኔታ መጠናከር አለበት ይህንን መሰረት አድርጎ ለመስራትም ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል ባይ ናቸው፡፡

ዘላለም ግዛው

Published in ፖለቲካ

በመላው ሀገሪቱ በስፋት እየተከናወነ ያለውን የኮንስትራክሽን እንቅስቃሴ ተከትሎ አጠቃላይ የግንባታ ግብዓት ፍላጎት ቀን ከቀን እየጨመረ ይገኛል። እድገቱን ተከትሎ የተፈጠረው የፍላጎትና የአቅርቦት አለመጣጣም ለዋጋ ጭማሪ ምክንያት ሲሆን ቆይቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግንባታ ብረት ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ ግን በመጠኑም ሆነ በድግግሞሹ ያሳየው ፍጥነት የኮንስትራክሽን ዘርፉን ብቻ ሳይሆን ተዛማጅ እንቅስቃሴዎችም እንዲቀዛቀዙ ምክንያት ሆኗል።ለመሆኑ የችግሩ ምንጭ ምንድነው?
«እያመረትን ያለነው ልናመርተው ከምንችለው በታች ነው። ይሄ የሆነው ደግሞ በውጪ ምንዛሪ እጥረት ነው» ያሉት የሲና ወንድማማቾች ብረታ ብረት ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ ወንድይፍራው በለጠ ናቸው። እንደ አቶ ወንድ ይፍራው ገለፃ ፋብሪካቸው በአመት 500 ሺ ሜትሪክ ቶን የአርማታ ብረት የማምረት አቅም ቢኖረውም አሁን እያመረተ ያለው ግን ከ24 በመቶ ብቻ ነው። ለምርት ግብአት ጥቅም ላይ የሚውለው ቁርጥራጭ ብረታ ብረት (እስክራፕ) በሀገሪቱ የሚገኘው በአመት ከሁለት መቶ ሺ ቶን አይበልጥም። ይሄን እንደ ግብአት የሚጠቀሙት ፋብሪካዎች ግን ከአስር በላይ ናቸው ለእያንዳንዱ ይዳረስ ቢባል እዚህ ግባ የሚባል ምርት ለማምረት የሚያስችል አይደለም። በመሆኑም ይሄን የሚተካ ከቻይና፣ ከህንድ፣ ከቱርክና ሌሎች ሀገራት ጠገራ ብረት ማስመጣት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የሲና ወንድማማቾች ብረታ ብረት ፋብሪካ ብቻ በአመት ከ150 እስከ 200 ሚሊዮን የሚደርስ የውጪ ምንዛሬ ያስፈልገዋል ብለዋል።
ስራ አስኪያጁ ጨምረው እንደገለጹት የዛሬ አመት ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ከብሄራዊ ባንክ ተፈቅዶላቸው የወሰዱት 40 ሚሊየን ዶላር ፋብሪካው ለተወሰነ ጊዜ ከገበያው ሳይወጣ እንዲቆይ ረድቶታል። ዘንድሮ ግን ከሶስት ሳምንት በፊት የተፈቀደላቸው 6 ሚሊየን ዶላር ብቻ ሲሆን በዚህ ገንዘብ ያዘዙት ጥሬ ዕቃ ወደ አገር ውስጥ ቢገባ እንኳን ከሳምንት የዘለለ ምርት ለማምረት የሚያስችል እንዳልሆነ ይገልፃሉ።በመሆኑም የውጪ ምንዛሪ ችግሩ የፋብሪካውን ህልውና እየፈተነው ነው።
ፋብሪካውን ገንብቶ ወደ ስራ ለማስገባት አንድ ነጥብ አራት ቢሊየን ብር ካፒታል የጨረሰ ሲሆን የዚህ ግማሽ የተሸፈነው ከመንግስት በተገኘ ብድር መሆኑም ሌላው ራስ ምታት ሆኖባቸዋል።እንዲሁም በአሁኑ ወቅት አንድ ሺ ቋሚ ሰራተኛ አሉ። ምርት በከፍተኛ ደረጃ በተቀዛቀዘበት ወቅትም ደመወዝ እየተከፈላቸው ነው።ይህም ሌላው ፈተና ነው።ከድርጅቱ ውጪ በሀገሪቱ ካለው ሰራተኛ 40 በመቶ በኮንስትራክሽንና ከኮንስትራክሽን ጋር በተያያዙ ተዛማጅ ስራዎች ተሰማርቶ ያለ ነው። በትንሹ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮግራም ብቻውን ከ30 ሺ ቶን በላይ የአርማታ ብረት ይፈልጋል። ይሄን ካላገኝ ምን ያህል ሰራተኞች ስራ ሊፈቱ እንደሚችል መገመቱ አይከብድም።
የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ፊጤ በቀለ እንደሚያብራሩት በመንግስት በኩል የቤት ልማትና የመንገድ ስራዎችን ጨምሮ ግዙፍ የግንባታ ፕሮጀክቶች በስፋት በመካሄድ ላይ ይገኛሉ። በግሉ ዘርፍ ያለው ኢንቨስትመንት የሚጠቀመው ብረትና ማህበረሰቡም ለተለያዩ ጥቃቅን ግንባታዎች የሚፈልገው የብረት መጠንም እየጨመረ ሄዷል። በአንጻሩ የሚቀርበው የብረት መጠን በቂና የተረጋጋ የገበያ ስርአትን የሚከተል አይደለም። ይህ አለመጣጣም የፈጠረው የዋጋ ጭማሪና የአቅርቦት እጥረት ህብረተሰቡን ለአላስፈላጊ ወጪና በአንዳንድ ቦታም ለግንባታ መጓተት እንዲሁም መቆም ምክንያት እየሆነ ከመጣ ውሎ አድሯል።
ለዘርፉ እንቅስቃሴ የተረጋጋ አለመሆን ምክንያት የሚሆኑት ጉዳዮችም እንደ ወቅቱ የተለያዩ ናቸው። እስከ 2007 ዓ.ም የዘርፉ ማነቆ ሆነ የቆየው የኃይል አቅርቦት እጥረት ነበር። ይሄ በአሁኑ ወቅት መቶ በመቶ ተፈቷል ባይባልም ለምርት እጥረት አልያም ለዋጋ መጨመር ሊያደርስ የሚችል ግን አይደለም። በሌላ በኩል በ2008 ዓ.ም ከፍተኛ ምርት ተመርቶ የነበረ ቢሆንም አምራቹንም ሆነ አስመጪውን ገበያ አለማግኘት ፈተና ሆኖባቸው ነበር። ከ2009 ዓ .ም እስከ አሁን ያለው ችግር ግን በቀዳሚነት ምንጩ ከውጪ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ ያጋጠመ የጥሬ እቃ አቅርቦት እጥረት ነው።
በአሁኑ ወቅት በሀገር ደረጃ ቅድመ ዝግጅታቸውን አጠናቀው በምርት ሂደት ውስጥ የሚገኙ አስራ ሁለት ፋብሪካዎች አሉ። እነዚህ ፋብሪካዎች ያሉባቸው ችግሮች ተቀርፈው በሙሉ አቅም ማምረት ቢችሉ በአመት 2 ሚሊዮን 163 ሺ ቶን የአርማታ ብረት የማምረት አቅም ይኖራቸዋል። በአንጻሩ በሀገሪቱ ያለው ፍላጎት ግን 1ነጥብ2 ሚሊዮን ቶን ነው። ይሄ የሚያሳየን ፋብሪካዎቹ በግማሽ አቅማቸው ቢሰሩ እንኳን አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ማሟላት ይችላሉ። ነገር ግን አሁን እየተመረተ ያለው ካለው አቅም ከፍተኛው አርባ በመቶ ብቻ ነው። ፋብሪካዎቹ ለምርታቸው ግብአትነት የሚጠቀሙት ጥሬ እቃ ከውጪ የሚመጣ በመሆኑ ከላይ የተቀመጠውን ማሳካት ካለ በቂ የውጪ ምንዛሪ የሚታሰብ አይሆንም። ይህም ሀገሪቱ በውጪ ገበያ ላይ እንድትንጠለጠል አድርጓታል ይላሉ ። አቶ ፌጤ በምሳሌነት ያነሱት ደግሞ በተያዘው አመት የመጀመሪያ ወራት በሀገር ውስጥ የተመረተው ምርት ከ100 ሺ ቶን በታች ሲሆን ከውጪ የገባው ግን ከ172 ሺ ቶን በላይ ነው። ይሄ ልዩነት በአሀዝ ብቻ ሳይሆን በዋጋ ደረጃም ሲነጻጸር ከውጪ የሚገባው ምርት አገር ውስጥ ካለው እስከ 30 በመቶ የሚደርስ ጭማሪ አለው።
አቶ ፊጤ እንዳሉት መንግስት ችግሩ በህብረተሰቡ ላይ ተጽእኖ እየፈጠረ መሆኑን በመረዳት የአገር ውስጥ አምራቾቹ ቅድሚያ የውጪ ምንዛሪ ሊያገኙ የሚችሉበትን አቅጣጫ አስቀምጦ ነበር። ከአመት በፊት ንግድ ሚኒስቴር፣ ብሔራዊ ባንክ፣ ፕላን ኮሚሽን፣ ባለሀብቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላትንም ውይይት ተደርጎ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሟል። በውይይቱም ብሔራዊ ባንክ አምኖበት ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ለአምራች ዘርፉ ቅድሚያ ምንዛሪ እንዲሰጥ ከስምምነት ለይ የተደረሰ ሲሆን ጥናት ተካሂዶ አንድ ነጥብ አራት ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ጥያቄ ቀርቦ ነበር። ከዘጠኝ ወር ቆይታ በኋላ ዘንድሮ በጥር ወር አካባቢ የተወሰነ ገንዘብ የተለቀቀ ቢሆንም ጥሬ እቃ ስላልነበራቸው የተሰጣቸው በቂ እንዳልሆነና ሊያሰራቸው የሚችል አለመሆኑንም አምራቾቹ በተደጋጋሚ ቅሬታ እያቀረቡ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከውጪ የሚመጡትም ምርቶች በውጪ ምንዛሪ እንደመሆኑ በዚህ ረገድ በርካታ ሊጣሩ የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉም ዳይሬክተሩ አንስተዋል።
በሌላ በኩል የአለም የብረት ዋጋ በፍጥነት የሚለዋወጥ ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ የዚህ ተጽእኖም በሀገር ውስጥ እንደሚንጸባረቅ ይናገራሉ። በተጨማሪም ለዋጋ መጨመር ከውጪ ወደ ሀገር ቤት የሚገቡት የግንባታ ብረቶች አዲስ አበባ ሳይገቡ በከተማዋ ዳርቻ እየተከማቹ እንደሆነ የሚገልፅና ለችግሩ ሰው ሰራሽ ምክንያቶችም እንዳሉ መረጃ እንደደረሳቸው ይናገራሉ። የዚህን ሂደት አጠቃላይ የመቆጣጠር ስራ የኢንስቲትዩቱ ባይሆንም ችግሩ በስሩ ካሉት አምራቾች ጋር ሊገናኝ ይችላል በሚል ጥርጣሬ ኃላፊዎችን ያካተተ የቁጥጥር ስራ ተሰርቷል። ሆኖም ግን በአምራቹ በኩል የተገኘ ነገር አለመኖሩን ጠቁመዋል።
የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን ኮርፖሬት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ግርማ አለማር በበኩላቸው ለችግሩ መባባስ አንዳንድ ኃላፊነት የጎደላቸው የብረት አስመጪዎች እንቅስቃሴም እንዳለበት ይገልጻሉ። የብረት እጥረት በከፍተኛ ደረጃ መከሰቱ መረጃው ደርሶናል ችግሩን ለማረጋጋትም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የብሔራዊ ኮሚቴው አባል በመሆን እየሰራ ይገኛል ብለዋል። የተወሰኑ የብረት አከፋፋዮች የውጪ ምንዛሪ ተመን ከመጨመሩ በፊት ያመጡትን ብረት ሀገር ውስጥ ከገባ በኋላ የውጪ ምንዛሪ ለውጥ ከተደረገ በኋላ ያለውን ተመን መነሻ አድርገው የሚሸጡ ነበሩ። ይህንንም በመቆጣጠር ቀድሞ በገባው ምርት ላይ ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ አድርገው እንዳይሸጡ የክትትልና የቁጥጥር ስራ ሲሰራ ቆይቷል። በዚህም ሂደት የተወሰኑ የብረት አስመጪዎች ክስ ተመስርቶባቸው በፍርድ ሂደት ላይ ይገኛሉ። የተወሰኑት ደግሞ በመድረክ በተደረገ ውይይትና በተደረሰ መግባባት የያዙትን ብረት በትክክለኛው ዋጋ ለገበያ እንዲያቀርቡና እንዲሸጡ ማድረግም ተችሏል።
አሁንም ቢሆን ግን ችግሩን በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው ገበያውን በመቆጣጠር ብቻ ሊሆን አይችልም። ይልቁንም አቅርቦቱን በከፍተኛ ደረጃ በመጨመር አንዳንድ አላስፈላጊ ጥቅም ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎችን የገበያው ሁኔታ አስገድዷቸው በተገቢው ዋጋ እንዲሸጡ ለማድረግ ብዙ ስራ የሚሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

 

ራስወርቅ ሙሉጌታ 

Published in ኢኮኖሚ

ባለፉት አስራ ሁለት ወራት የአፍጋኒስታን የፀጥታ ሃይሎች እየተዳከሙ መምጣታቸው ዓለማችን ሠላም እየራቃት በመጣበት በዚህ ወቅት ትልቅ ቀውስ መሆኑ በርካቶች ስጋት ሲገልፁ ይሰማል። በነዚህ ጊዜያት የአፍጋኒስታን የጦር ሃይል አስር በመቶው መቀነሱ ወይንም ሦስት መቶ ሺ ወታደሮች ከጦሩ ውጪ መሆናቸውን የዴይሊ ቴሌግራፍ ሪፖርቶች ያመለክታል።
ከቀናት በፊት አርባ ሰዎች የተገደሉበትን ጥቃት ተከትሎ የወጡ ሪፖርቶች እንዳመለከቱት የአፍጋኒስታን ጦር አቅሙ እየከዳው በሄደበት በዚህ ወቅት የአሸባሪው ቡድን አይ ኤስ አይ ኤስ እያንሰራራ በርካታ ግዛቶችንም በእጁ እያስገባ ይገኛል። ይሁን እንጂ የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ጉዳዩን በማስተባበል ታጣቂዎችን ለመዋጋት የሚያስችል በቂ ወታደር እንዳላቸው ገልፀዋል። የወታደሮቹ የሙያ ስነምግባርና ስብዕና ከፍተኛ መሆኑን በመግለፅም በመላው አፍጋኒስታን አሥራ አንድ ዘመቻዎችን ከፍተው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
ቃል አቀባዩ ይህን ይበል እንጂ ዓለም አቀፍ ተቋማት እያወጡት የሚገኘው ሪፖርት ተቃራኒ ነው። እንዲያውም የአገሪቱ መንግሥት እየመራሁ ነው ይበል እንጂ አፍጋኒስታንን እያስተዳደረ የሚገኘው ታሊባን መሆኑን በቅርብ የወጡ መረጃዎች አስረግጠው ይናገራሉ።
ሮይተርስ ምንጮችን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ መሰረት ታሊባንና በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች አስራ አራት ነጥብ አምስት በመቶ አፍጋኒስታንን ተቆጣጥረዋል። ይህም ማለት አራት መቶ ሰባት የአገሪቱ አውራጃዎች ላይ እንደፈለጉት እያዘዙ ይገኛሉ። ይህም ከ2015 ወዲህ ከፍተኛ ቁጥር ሆኖ ተመዝግቧል።
አይደለም የአፍጋኒስታን መንግሥት የአሜሪካን መራሹ ጦር ታሊባን ላይ ጠበቅ ያለ ዘመቻ ከጀመረ የሰነበተ ቢሆንም እስካሁን ድል ማድረግ አልተቻለውም። አሜሪካን ከሰባ ስምንት ቢሊየን ዶላር በላይ በማፍሰስ የቡድኑን አከርካሪ ለመምታት እያደረገች ያለው ጥረት ኪሳራን እንጂ ቅንጣት ታህል ትርፍ እንዳላመጣላት እየተስተዋለ መሆኑን ተንታኞች ይናገራሉ።
በርካታ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት ሰባ በመቶ የአፍጋኒስታን የቆዳ ስፋት ላይ ታሊባን እንደፈለገው ወጥቶ መግባት የሚችልበትን አቅም ፈጥሯል። ታሊባን እንዲህ ጉልበቱ ሊፈረጥም የቻለውም በገንዘብ ረገድ ቱጃር ታጣቂ ቡድን በመሆኑ ነው ይላሉ። ታሊባን በሦስት መቶ ሃያ ስምንት ሺ ሔክታር መሬት ላይ ሄሮይን የተባለውን አደንዛዥ እፅን የሚያመርት ሲሆን ሰማንያ አምስት በመቶ የዓለም አደንዛዥ እፅ ምርትን የሚቆጣጠር በመሆኑ የሚያገኘው ረብጣ ገንዘብ ከተራ አሸባሪ ቡድን የላቀ አድርጎታል። ሃያሏ አሜሪካ ሳትቀር ባለፈው 2017 ከስምንት ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪ አድርጋ የዚህን ቡድን ጉዞ ማቆም አልተቻላትም። የአፍጋኒስታን ፕሬዚዳንት አሻር አፍጋሃኒ አስተዳደርም ቢሆን የሚክደው አይደለም።
አንዳንድ ተንታኞች እንደሚናገሩት ፕሬዚዳንት አሻር አፍጋሃኒ በአፍጋኒስታን የአደንዛዥ እፅ ሽያጭ ባይኖር በአጭር ጊዜ ውስጥ ጦርነቱ ያበቃል ብለው ያምናሉ። ታሊባን በተቆጣጠራቸው ቦታዎች ላይ ሰፋፊ የአደንዛዥ እፅ እርሻዎች እንዳሉት መረጃዎች ይጠቁማሉ። ሠላም ለማስከበር በዚህች አገር የሚገኙ የአሜሪካ ኮማንደሮች ሳይቀሩ ከአደንዛዥ እፁ ሽያጭ እጃቸው ንፁህ እንዳልሆነ ይነገራል። በዚህም የታሊባን ወታደሮች በወር ውስጥ ብቻ በሚሊየን የሚቆጠር ዶላር ለመስራት አይቸገሩም።
የታሊባን አመራሮች ይህንን በማስተባበል የሚያመርቱት አደንዛዥ እፅ እንደሌለ በተለያዩ ጊዜዎች ይናገራሉ። እውነታው ግን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአደንዛዥ እፅና የወንጀል ቢሮ እንደሚለው ታጣቂው ታሊባን ይቅርና የአፍጋኒስታን መንግሥት ራሱ ኢኮኖሚውን የሚደጉመው ኦፒዮን በተባለው የአደንዛዥ እፅ ምርት ነው። ለምሳሌም አፍጋኒስታን በ2016 ኦፒዮን ገበያ ላይ አውላ ሦስት ቢሊየን ዶላር ወደ ካዝናዋ ማስገባት መቻሏ ይታወቃል። ይህም ማለት የአገሪቱን አሥራ ስድስት በመቶ የብሔራዊ ምርት እድገት የሚወክል ሲሆን ከ2015ቱ ጋር ሲነፃፀር ከእጥፍ በላይ የላቀ ነው።
አሜሪካ አፍጋኒስታን ላይ የምትወስደው እርምጃ ፀሃይ የሞቀ ሃቅ ቢሆንም በህገ ወጥ መንገድ አደንዛዥ እፁን በዋናነት የምትረከበው ራሷ አሜሪካ ሆና መገኘቷ ብዙዎችን ያስገረመ ጉዳይ ነው። ጉዳዩ ውስብስብና ብዙ ሴራዎች ያሉበት ከመሆኑ ባሻገር ተውባይ አለመኖሩ ችግሩ መፍትሄ እንዳያገኝ ማድረጉን ተንታኞች ይናገራሉ። በተጨማሪም ታሊባን በረብጣ ዶላሮች የሌሎችን ልብ ማሸፈት መቻሉ የትኛውንም አካል በቀላሉ እንዲያንበረክክ አድርጎታል።
ታሊባን ከአደንዛዥ እፅ ይልቅ አስፈሪ ያደረገው ሃያላኑን መከፋፈል መቻሉ እንደሆነ በርካታ የፖለቲካ ምሁሮች አስተያየት ሲሰጡ ይደመጣሉ። አፍጋኒስታንን አሜሪካን፤ ሳውዲ አረቢያና ምዕራባውያኑ ሲደግፉ ታሊባን ከኢራንና ሩሲያ ድጋፍ ያገኛል። ቡድኑ ለዚህም ነው እስካሁን እጅ ያልሰጠው እንጂ የአደንዛዥ እፅ ጉዳይ ብቻ አይደለም።
ታሊባን የገንዘብ አቅሙ ደጋፊዎችን አፈራለት እንጂ በሽብር ረገድ ከአልቃይዳ የበለጠ ሆኖ አይደለም የሚሉ ተንታኞችም ጥቂት አይደሉም። እዚህ ላይ ታሊባን በአንድ ወቅት የአፍጋኒስታን መንግሥት አካል እንደነበረ በማስታወስም ተራ የአሸባሪ ቡድን እንዳልሆነ ያስቀምጣሉ። ታሊባን የጦር መሳሪያ ሽያጭ እንድታደርግለት ዘወትር ደጅ የሚፀናባት ሩሲያ ቡድኑ መንግሥት በነበረበት ወቅት በጠላት አይን ይመለከታት እንደነበር ይታወቃል። ታሊባን አሁን ላይ አካሄዱን አስተካክሎ ከሩሲያ ጋር ለመሻረክ መሞከሩ ቡድኑ በተጠና ሴራ የሚጓዝ እንጂ እንደሌሎች የሽብር ቡድኖች እዚህም እዚያም የቦንብ ናዳ በህፃናት ላይ የሚያወርድ አለመሆኑን ተንታኞች ያስረዳሉ።
አይ ኤስ አይ ኤስ የአፍጋኒስታንን ምድር ሲረግጥ ታሊባን እንደማንኛውም የሽብር ቡድን ከሆነ ለምን መቆጣት አማረው? የሚሉ የፖለቲካ ምሁራን በርካታ ናቸው። አይ ኤስ አይ ኤስ ከሶሪያና ኢራቅ የወጣው አገራቱ በነበራቸው ጥንካሬ ሳይሆን ለሌላ ሴራ ተፈልጎ በአፍጋኒስታን ይሁንታ በማግኘቱ እንደሆነም ያስቀምጣሉ። እዚህ ላይ አይ ኤስ አይ ኤስ ወደ አፍጋኒስታን ሲገባ የታሊባንን ያህል እንኳን ከአገሪቱ መንግስት ተቃውሞ እንዳልገጠመው ያነሳሉ።
በተጨማሪም አይ ኤስ አይ ኤስ ታጣቂ ቡድን ከሆነ በሚፈፅመው ጥቃት እየመረጠ የሺሃ ማህበረሰብን ማጥቃት ፈለገ? የሚለው ጥያቄም ይነሳል። ለዚህም ጥያቄ ከበስተጀርባ ትልቅ ሴራ እንዳለ ይገለፃል። ይህም በአፍጋኒስታን ሃያላኑ አገራት መከፋፈላቸው በምክንያትነት ይቀመጣል። አይ ኤስ አይ ኤስን እንደሚደግፉ ማስረጃ ማቅረብ ከባድ ቢሆንም አሜሪካ፤ ሳውዲ አረቢያና ምዕራባውያን አፍጋኒስታን ውስጥ አይፈልጉትም ለማለት አይቻልም። ኢራን አይ ኤስ አይ ኤስን እንደ ጠላቷ አድርጋ ትቆጥረዋለች፤ በአፍጋኒስታን አስተምህሮቷ እንዳይኖር ደጋፊዎቿን ለይቶ እየገደለ መሆኑ አንድ ማሳያ ነው። ለዚህም ባሳለፍነው ሳምንት የነበረው ጥቃት በሺዎች ላይ ያነጣጠረ ሲሆን በመዲናዋ ካቡል የቢቢሲውን ጋዜጠኛ አህመድ ካቡን ጨምሮ አርባ ሰዎች መገደላቸው በምክንያትነት ይቀመጣል።

ቦጋለ አበበ

Published in ዓለም አቀፍ


የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተነድፎ ወደ ተግባር ሲገባ የተለያዩ መነሻዎች የነበሩት ቢሆንም ዋናው አጀንዳ ግን ተከታታይነት ባለው ሁኔታ መመዝገብ የጀመረውን የግብርና ምርትና ምርታማነትንም ሆነ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገቱን በማስቀጠል የአርሶ አደሩን ብሎም የመላውን ህዝብ ተጠቃሚነት ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር መሆኑ ይታወቃል፡፡
ዛሬ ከዝናብ ጥገኝነት በመውጣት መስኖን መሰረት ባደረገው የግብርና ሥራ ኢትዮጵያ በግብርና ምርቶች በዓይነት፣ በጥራት እና በመጠን ተወዳዳሪ ሆና በዓለም የግብርና ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ሚና እንዲኖራት በማስቻል በጥሩ ሂደት ላይ የምትገኝ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ለዓለም ገበያ በመጠንና በጥራት ተወዳዳሪ ሆና የውጭ ምንዛሬ ግኝቷን የምታሳድግበት አቅጣጫም ተዘርግቷል። ለዚህም አርሶ አደሮች ገበያ ተኮር ምርቶች ላይ እንዲያተኩሩ ማስቻል፣ በእንስሳት ዘርፍ ያለውን የምርምር ሥራዎች ማጠናከር እና ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች ሁለንተናዊ የግብርና ምርምር ሥራዎች እየተከናወነ ነው።
የግብርናው ዘርፍ ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው ሽግግር ዋነኛ ሞተር በመሆኑ የግብርና ልማቱን ለማገዝ ወቅታዊ፣አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና እውቀቶች እየቀረቡ ነው። ለጋራ አገራዊ የልማት ግብ ስኬትም የምርምር አቅምና ብቃትን ማሳደግ እና አዋጭ ቴክኖሎጂዎችን ለተጠቃሚዎች የማቅረብ ሥራ እየተፋጠነ በመሆኑ የሁለተኛውን ዙር ጉዞ ፈጣንና ውጤታማ እንደሚያደርገው መገመት አይከብድም።
የሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ከተጀመረበት ማግስት ጀምሮ በመላው አገሪቷ የሚገኙ አርሶአደሮች በየጓሯቸው የሚገኙ ቅጠላ ቅጠሎችንና ተረፈ ምርቶችን እንዲሁም ሌሎች በየአካባቢያቸው የሚገኙ ቁሳቁሶችን በመጠቀም የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ምርትና ምርታማነታቸውን እጥፍ ድርብ ማድረስ መቻላቸው ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም ካስቻሉና የአርሶአደሩን ተነሳሽነት በከፍተኛ ደረጃ ካሳደጉ ምክንያቶች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ጉዳዩ አሁን ይህ እንቅስቃሴ እንዳይቋረጥ የሚያስችሉ መንገዶችን መከተል ነው። ከነዚህም መካከል አሁን ያለንበት ወቅት የመኸር ዝግጅት የሚደረግበት በመሆኑ ከፍተኛ ሥራ ይጠበቃል።
በእነዚህና መሰል በሆኑ የግብርና እንቅስቃሴዎች የሚገኙ ውጤቶችን መነሻ በማድረግ የገጠር ወጣቶችን በግብርና ማቀነባበሪያው ዘርፍ በስፋት ማሳተፍ ከተቻለ በእቅድ ዘመኑ ሃገሪቱ የጣለችው አጠቃላይ የልማት ግብ መነሻና መድረሻውም ይኸው ስለሆነ የሃገሪቱ ህዳሴ በማይነቃነቅ አለት ላይ መሠረቱን የሚጥል ይሆናል፡፡
ዝናብ አጠርና እርጥበታማ በሆኑ አካባቢዎችም በተደጋጋሚ የሚከሰቱ የድርቅ አደጋዎችን መከላከል የሚያስችል ስርዓት መዘርጋቱ ሌላውና ስለተደረሰበት አቅም ለማስላት አስረጅ ሆኖ ሊጠቀስ የሚገባው ነጥብ ነው ። ይህ ስርዓት ልማታዊ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ነው። ባሳለፍነው ዓመት የተከሰተውንና ያለብዙ የውጪ እርዳታ መቋቋም የተቻለውን የድርቅ አደጋ ብናስታውስ በፕሮግራሙ ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎች ባፈሩት ጥሪት የተፈጠረውን ችግር መቋቋም ተችሏል። ይህም ተከስቶ በነበረው ድርቅ ሳቢያ ይፈጠር የነበረን ችግር መቋቋም የሚያስችል አቅም መገንባቱን ያሳያል። ከእነዚህ ስኬት በስተጀርባ ያለው ምስጢር የህብረተሰቡ ሰፊና የተደራጀ ንቅናቄና ተሳትፎ ነው፡፡ በዚህ መኸርም ይኸው ንቅናቄ ተጠናክሮ እስከቀጠለ ድረስ ብቻ ነው፤ የሁለተኛውን ዙር እቅድ በስኬት ማጠናቀቅ የሚቻለው።
ቀጣዩ የትራንስፎርሜሽንና ዘላቂ ልማት ዕቅድ ዘመን በአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ላይ የተመሠረተ የግብርና ልማት በማፋጠን ይልቁንም እያንዳንዱ የምርት ዘመን ላይ መኸር ከበልግ ሳይለይ ጠንክሮ መስራትን የሚጠይቅ ነው። ይህ ብቻ አይደለም የተማሩ ወጣቶችን በማደራጀት በግብርና ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ በማድረግ፣ አገራዊ እና የተመረጡ የውጭ የግል ባለሃብቶች እንደየ ችሎታቸው በከፍተኛ ደረጃ እንዲሳተፉ በማድረግ በሰብል፣ በአበባ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በእንስሳት ሃብት ልማት ዘርፎች ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት የሚሰራበት የእቅድ ዘመን መሆኑም ተመልክቷል፡፡
በመሆኑም የአነስተኛ አርሶና አርብቶ አደሩ ግብርና አሁንም ዋናው የግብርና ዕድገት መሠረት ሆኖ እንዲቀጥልና የአነስተኛ አርሶና አርብቶ አደሩ ግብርና ፈጣን እድገት እንዲያረጋግጥ የማስፋት ስትራቴጂውን አሟልቶ መተግበር፣ የልማት ቀጠናዎችን መሠረት ያደረገ የግብርና ልማት መከተልና ሌሎች በግብርና ግብዓትና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዙሪያ ያሉ ችግሮችን መፍታት ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ የወቅቱን የወጣቶች ጥያቄ በተሟላ መልኩ መመለስ የሚቻለውም በእዚህና ግብርናን መሰረት ባደረገው የገጠር ሥራዎች ብቻ ነው። በተመሳሳይ የግል ባለሀብቱ በግብርና ልማት ላይ የሚኖረው ድርሻ ከፍ እንዲል በማድረግ አገሪቱ ለያዘችው ልማትና ከድህነት ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት እንዲያግዝ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል፡፡
የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን በማጎልበት አስተማማኝ የግብርና ልማት ለማረጋገጥ እንዲቻል የግብርና ልማት ዕቅዶች በይዘትም በትግበራም ከአረንጓዴ ልማት ራዕይ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ማስቻል ከዚሁ ጋር የመስኖ ልማትን ማስፋፋት ሌሎች በእቅድ ዘመኑ የተያዙ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ስለሆነም የብዝሀ ህይወት ጥበቃን ከዚሁ ጋር አያይዞ በማጠናከር የማኅበረሰቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የተመለከተ የወቅቱ ጥያቄ በተሟላ መልኩ መመለስ ይቻላል።
የአርሶ አደሩን ገቢ በፍጥነት ለማሳደግ አርሶ አደሩ የላቀ ዋጋ ወዳላቸው ምርቶች ማምረት እንዲሸጋገር ማድረግና የግብርና ግብይትን በተቀላጠፈ አካሄድ ተግባራዊ ማድረግ፣ በገጠር ፈጣን ዕድገት የሚፈጥረውን ዕድል በመጠቀም የወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በድርቅ የማይንገዳገድ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያስችላል፡፡
ለሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካትና መሠረታዊ አቅጣጫዎቹን ለመተግበር አስፈላጊ የሆኑ ስርዓቶችን አሟልቶና ከፊል ቆላና ቆላማ በሆኑ አካባቢዎች የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የኑሮ ማሻሻያና የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ የሚያረጋግጡ ሥራዎችን መስራት ያስፈልጋል።
የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የግብርና ዘርፍ ዋና ዓላማ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ የግብርና ልማትን መሠረት ያደረገ በዘርፉ ፈጣንና ዘላቂነት ያለው ዕድገት በማምጣት የህዝቡን ተጠቃሚነት በየደረጃው ማረጋገጥና በአጠቃላይ ኢኮኖሚውና በዘርፉ ደረጃ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲመጣ ማስቻል ነው፡፡ በተጨማሪም የዘርፉን ምርታማነት በማሳደግ ለኢኮኖሚው የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ማሳደግና ለማክሮ ኢኮኖሚው መረጋጋት ያለውን ወሳኝ ሚና መጫወት የሚያስችል የማምረት አቅም መገንባት ነው፡፡
በዘርፉ የሴቶችና የወጣቶችን እንዲሁም የዘርፉን ተዋናዮች በተደራጀ አግባብ በማሳተፍ ለልማቱ የሚጠበቅባቸውን እንዲያበረክቱና ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ የዘርፉ ዋና ዋና ዓላማዎች ናቸው፡፡ ይህን ማሳካት የሚቻለው ደግሞ እራሳቸው ወጣቶችን እና ሴቶችን በማሳተፍ ብቻ ነው።
በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የአርሶ-አደርና የአርብቶ-አደር ምርታማነትን ለማሳደግና የምርት ጥራት ለማረጋገጥ የተጀመረው ሥራ በዘርፉ ትራንስፎርሜሽን እንዲያመጣ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል የሚባለው ያለምክንያት አይደለም፡፡ ከአነስተኛ አርሶ-አደር ማሳ በመኸር ወቅት የሚገኘውን የሰብል ምርት በ2007 ከነበረበት 270.3 ሚሊዮን ኩንታል 2012 ላይ ወደ 406 ሚሊዮን ኩንታል ለማሳደግ መታቀዱ ተመልክቷል፡፡
የዋና ዋና የሰብል ዓይነቶች ምርታማነትና ምርት ትንበያ ግቦችም በእቅዱ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ የአገዳ ሰብል ምርታማነትን በመነሻ ዓመት (2007) ከነበረበት 29 ኩንታል በሄክታር በ2012 ወደ 42 ነጥብ 64 ኩንታል በሄክታር በማሳደግ አጠቃላይ ዓመታዊ ምርቱን በመነሻው ዓመት (2007) ከነበረበት 115 ሚሊዮን ኩንታል በ2012 ወደ 171 ነጥብ 78 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ ዕቅድ ተይዟል፡፡
የብርዕ ሰብል ምርታማነትን በመነሻው ዓመት (2007) ከነበረበት 21 ነጥብ 1 ኩንታል በሄክታር በ2012 ወደ 31 ኩንታል በሄክታር በማሳደግ አጠቃላይ ዓመታዊ ምርቱን በመነሻው ዓመት (2007) ከነበረበት 120 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በ2012 ወደ 184 ነጥብ 22 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚደርስም ታቅዷል፡፡
በጥራጥሬ ሰብል ምርታማነት በመነሻው ዓመት (2007) ከነበረበት 17 ነጥብ 2 ኩንታል በሄክታር በ2012 ወደ 23 ኩንታል በሄክታር በማሳደግ አጠቃላይ ዓመታዊ ምርቱን በመነሻው ዓመት (2007) ከነበረበት 26 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በ2012 ወደ 38 ነጥብ 75 ሚሊዮን ኩንታል ይደርሳል ተብሏል፡፡
የቅባት ሰብል ምርታማነት በመነሻው ዓመት (2007) ከነበረበት 9 ኩንታል በሄክታር በ2012 ወደ 12 ነጥብ 7 ኩንታል በሄክታር በማሳደግ አጠቃላይ ዓመታዊ ምርቱን በመነሻው ዓመት (2007) ከነበረበት 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በ2012 ወደ 11 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ እንደሆነ በእቅዱ ግብርናን የተመለከተው ክፍል በሚገባ ተመልክቷል።
የዋና ዋና ሰብሎችን ምርታማነትና ምርት የማሳደግ ዋናው ጉዳይ የአብዛኛውን አርሶ አደር የምርታማነት መጠን ምርጥ አርሶ አደሮች ከደረሱበት ደረጃ ማድረስ መሠረታዊ ግብ ነው፡፡ ይህም በዋና ዋና የምግብ ሰብሎች፣ የፋብሪካ ግብዓቶች እና የኤክስፖርት ሰብሎችን ያካትታል፡፡ ይህ መሠረታዊ ግብ እንደተጠበቀ ሆኖ በተከታታይ የሞዴል አርሶ-አደሮች ምርታማነት ደረጃ ላይ የደረሱ በርከት ያሉ አርሶ-አደሮች ያሉ በመሆኑ የግብርና ምርምር ተቋማትን አቅም በማጐልበትና በማበረታታት እነዚህ አርሶ-አደሮች ወደ ግብርና ምርምር ተቋማት የምርታማነት ደረጃ እንዲቀራረቡ ተጨማሪ ፓኬጆች በማዘጋጀት መረባረብ እንደሚገባ ያሳያል፡፡ ይህ እንደሁለተኛ ግብ ሊወሰድ የሚገባው ተግባር ነው፡፡
በሦስተኛ ደረጃ የተያዘው ግብ የግብርና ምርምር ተቋማት ለቀጣይ ምዕራፍ የግብርና ዕድገት ምንጭ የሚሆኑ ቴክኖሎጅዎችን በማዘጋጀት እንዲረባረቡ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ መስጠትና ማብቃት ይሆናል፡፡ ስለሆነም የዓለም አቀፍ ቤንች ማርኪንግ በማስቀመጥ የግብርና ምርምር ተቋሞች ወደ እዚሁ ደረጃ እንዲደርሱ መሥራት የሚገባ ይሆናል፡፡
ግብርናችን በቀጣይነት ያለማቋረጥ እያደገ በመምጣቱ ለአደጋ ተጋላጭነታችንና ድርቅን የመቋቋም አቅማችን እንደ አገር እየተገነባ የመጣበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ከአካባቢ አካባቢ የተለያየ አፈፃፀም ያለና አሁንም ለአየር ንብረት መዛባት ተጋላጭነት ያላቸው አካባቢዎች ያሉን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ጠንከር ያለ ድርቅ ቢከሰት አንኳን ችግሩን ተቋቁሞ የማለፍ አቅማችን እያደገ መጥቷል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ አገሪቱ በግጭትም ውስጥ ሆና ያስመዘገበችው የግብርና ውጤት ከቀደሙት የቅርብ ዓመታት ልቆ መገኘቱ ከግጭት የሚያጸዱ አሰራሮች ተዘርግተው ቢሆን ኖሮ የሚያስብሉና የልፋታችንን ያህል እንዳናገኝ እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን ሁሉ በፍጥነት ማስወገድ እንዳለብን የሚያስገነዝቡ ናቸው። ስለሆነም ሠላማችንን ከማስጠበቅ ጀምሮ የወጣቱን ጥያቄ መመለስ የሚቻለው ወጣቱን ሁሉ ዓቀፍ በሆነ መልክ በእያንዳንዷ የግብርና ሥራዎች ላይ በማሳተፍ ብቻ የመሆኑን እውነታ ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ ማድረግ ይገባል።


ስሜነህ

Published in አጀንዳ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።