Items filtered by date: Sunday, 06 May 2018

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማደረግ ከሰዓት በኃላ ወደ ኬንያ ያቀናሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኬንያ የሁለት ቀን ቆይታቸው ከኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና ከሌሎች የሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር በሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት አና በቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ያደርጋሉ ተብሏል፡፡

በናይሮቢ በሚናራቸው ቆይታም ስኬታማ የሆኑ ዲፕሎማሲያዊ እና የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ጉዳዮች ዙሪያ በመወያየት ከሀገሪቱ ጋር ከስምምነት ላይ እንደሚደርስ ይጠበቃል ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኬንያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እንዲያደርጉ ከኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ግብዣ እንደቀረበላቸው ይታወሳል።

የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞኒካ ጁማን ናቸው በያዝነው ሚያዚያ ወር መጀመሪያ ላይ የግብዣ ደብዳቤውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ይዘው የመጡት።

በወቅቱም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይና የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞኒካ ጁማን በሁለቱ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጎረቤት ሀገራት እያደረጉ ባሉት ጉብኝቶች እስካሁን በጂቡቲ እና በሱዳን ስኬታማ ጉብኝቶችን ማድረጋቸው ይታወሳል።

በእነዚህ ሀገራት በነበራቸው ቆይታም ኢትዮጵያን ከየሀገራቱ ጋር በኢኮኖሚ የሚያስተሳስሩ እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ የተለያዩ ስምምነቶች መደረሳቸውም ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በጂቡቲ በነበራቸው ቆይታም ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማርጊሌህ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

በተጨማሪም በመሰረተ ልማት፣ በባቡር፣ በመንገድ፣ በኤሌክትሪክ እና በውሃ ዘርፍ ያለውን ትስስር የበለጠ ለማጠናከር መስማማታቸው ይታወሳል።

በተለይም ኢትዮጵያ የጂቡቲ ወደብ ዋነኛ ተጠቃሚ እንደመሆኗ የጂቡቲ ወደብን በጋራ ለማልማትና ለማስተዳደር ከስምምነት ተደርሷል።

በሱዳን ባደረጉት ይፋዊ የስራጉብኝትም ተጨማሪ ሶስት አዳዲስ መንገዶችን ለመገንባትና አዲስ አበባና ካርቱምን የሚያገናኝ

የምሰራቅ አፍሪካ ማዕከል የሆነ የባቡር መሥመር ለመዘርጋት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወቃል።

በተመሳሳይ በድንበሮች አካባቢ ነጻ የንግድ ቀጠና ለመፍጠርና የሱዳን ወደብን በጋራ ለማልማትና ለማስተዳደር የተደረሰውም ስምምነት ሌላው የጉብኝቱ ስኬት መሆኑን ጠቁመዋል።

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይም ሁለቱ አገራት ተመሳሳይ አቋም ያላቸውና ግድቡ በተለይም ለቀጣናው አገራት በሚሰጠው ጥቅም ላይ ትኩረት አድርገው መወያየታቸውን ታውቋል፡፡

Published in የሀገር ውስጥ
Sunday, 06 May 2018 20:12

የአሸናፊነት ተምሳሌት

ወደ አራት ኪሎ የድል ሐውልት የሚወስዱ መንገዶች በአራቱም ማዕዘን ግራና ቀኝ የሚታየው በተለያየ አልባሳት የደመቁ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ እንደ ወትሮው የተሽከርካሪ ትርምስና ጩኸት የለም፡፡ በየአቅጣጫው የሚሰማው አባት አርበኞችን የሚያወድስ ህብረ ዝማሬ ነው፡፡ እዚህ ጋ ለነፃነት የተጋደሉ ጀግኖችን ፎቶ የያዘ ቲሸርት የለበሱ ወጣቶች በቡድን ቡድን ሆነው ህብረ ዝማሬ ያሰማሉ፡፡ እዚያ ጋ ደግሞ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን አልባሳት የለበሱ ወጣቶች የጀግኖችን ስም እየጠሩ፣ እንደ አባቶቻቸው ጦር እየሰበቁ ይፎካራሉ፡፡ ወደ አደባባዩ ውስጥ ጠጋ ስንል ደግሞ ገና የአርበኝነት ወኔያቸው ያልለቀቃቸው አርበኞች ጦራቸውን እየሰበቁ ሲፎክሩ ይታያል፡፡ 

ኢትዮጵያውያን አርበኞች ፋሺስት ጣሊያን ከአገራቸው ያባረሩበትን 77ኛውን የአርበኞች ድል መታሰቢያ ለመዘከር ገና ከማለዳው ጀምሮ ዙሪያውን በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ደምቆ የነበረው የአራት ኪሎ የድል ሐውልት አደባባይ እየረፈደ ሲሄድ በአራቱም አቅጣጫ መፈናፈኛ አልነበረውም፡፡ በአደባባዩ ላይ ያለውን ትዕይንት ለማየት ዳርዳሩን ያሉ ወጣቶች አንዱ በአንዱ ትክሻ ላይ ሲንጠራሩ ይታያል፡፡ የአባት አርበኞች ሽለላና ፉከራ ቀልባቸውን ሲስበው በየደረጃውና በአካባቢው ባለው የብረት ድልድይ ላይ ሆነው የሚመለከቱ ወጣቶች በወኔ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ከአባቶች ጋር ይፎክሩ ነበር፡፡ ከትምህርት ቤቶች፣ ከተለያዩ ክበባትና ማህበራት በቡድን የመጡ ወጣቶችም ለበዓሉ ከፍተኛ ድምቀት ሰጥተውታል፡፡
አንዲት ወጣት ግጥም ልታቀርብ ወደ መድረኩ ተጋበዘች፡፡ መድረኩ ላይ እንደወጣችም  በሽለላ ዜማ የጀግኖችን ስም እየጠራች ግጥሟን ጀመረች፡፡ ይህኔ ነበር የአባት አርበኞች ስሜት ገንፍሎ መድረኩን ፉከራ በፉከራ ያደረገው፡፡ የልጅቷ ግጥም ለጊዜውም ቢሆን ቆም አለ፤ ምክንያቱም በሽለላ ዜማ የጀመረችው ግጥም አንድም አባት አርበኛ እንዲቀመጥ አላስቻለም፡፡ ወደቦታቸው ሲቀመጡ በምርኩዝ የሄዱት አባት አርበኞች ወኔያቸው ሲቀሰቀስ ምርኩዙ ምርኩዝ መሆኑ ቀረና እንደ ጦር እየሰበቁ መፎከሪያ አደረጉት፡፡ ጸጉራቸው ነጭ ብቻ የሆነና ሰውነታቸው በእርጅና የተጎዳ የሚመስሉ አርበኞች እንደዚያ ሲሽከረከሩ ያየ የራሱም ወኔ ይተናነቀዋል፡፡ ከርቀት ሆነው የሚከታተሉ ሁሉ ባሉበት ሲፎክሩና ሞራል ሲሰጡ ይሰማል፡፡ በአባቶች ፉከራ ታጅቦ የልጅቷ ግጥም ግማሹ እየተሰማ ግማሹም በፉከራ እየተዋጠ አለቀ፡፡
ወጣት ሳምሶን አለማየሁ ይህን ትዕይንት ከተከታተሉ ወጣቶች አንዱ ነው፡፡ ሳምሶን እንደሚለው ታሪካዊ በዓላት በእንዲህ ዓይነት ዝግጅት መከበራቸው በወጣቶች ዘንድ መነቃቃት ይፈጥራል፡፡ በተለይም የአራት ኪሎ የድል ሐውልት አደባባይ ብዙ ወጣቶች የሚታዩበትና ታሪካዊ ቦታ ነው፡፡ ቢያንስ በዚህ አካባቢ ያለፈ ወጣት እንኳን «ይሄ ምንድነው» ብሎ መጠየቁ አይቀርም፤ የአርበኞች ቀን ማለት ወራሪው ፋሽስት ጣሊያን ከኢትዮጵያ ተጠራርጎ የወጣበት ቀን መሆኑን ያውቃል፡፡ ለታሪክና ለአገር ፍቅር መነሳሳትን ይፈጥራል፡፡
እንዲህ ዓይነት ታሪካዊ በዓላት በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ትኩረት እየተሰጣቸው እንደሆነ ያስተዋለው ወጣት ሳምሶን፣ አንድ የታዘበው ነገር እንዳለም ይናገራል፡፡ አባት አርበኞች «ለጠላት አንንበረከክም» ብለው አገሪቱን ከነክብሯ አስረክበዋል፡፡ ባህሏና ቋንቋዋ በውጭ ወራሪ ሳይበረዝ ያስረከቧትን አገር አሁን አሁን ወጣቱ ላይ በውጭ ፋሽን መወረሩ ሌላኛው ቅኝ መገዛት እንዳይሆን ይፈራል፡፡ «ይህን የድል በዓል ለማክበር ድንቅ የሆኑ የአለባበስ ውበት፣ የራሳችን ቋንቋ እያለን የውጭ ፋሽን አድናቂ መሆናችን ሊስተካከል ይገባል» ሲል ያሳስባል፡፡
ተማሪ ዘሪሁን ተሾመ በዓሉን ለማክበር ከመጡት መካከል አንዱ ነው፡፡ እርሱ እንደሚለው፣ ይህን በዓል ለማክበር በህብረ ዝማሬ፣ በመጣጥፍና መፈክሮችን በማዘጋጀት ሂደት ውስጥ ብዙ ነገር እንዲያውቅ አድርጎታል፡፡ እንዲህ ዓይነት በዓላት በተማሪዎች እንዲዘጋጁ መደረጉም በዓሉን እንዲያውቁት ያደርጋል፤ ስለአገራቸው ታሪክ እርስበርስ እንዲወያዩና የአባቶቻቸውን ወኔ በመቅሰም የአሸናፊነት ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡
ወኔ ውስጣቸውን እየቀሰቀሰው ጦራቸውን እየሰበቁ ሲፎክሩ ወደነበሩት አንድ አባት አርበኛ ጠጋ አልኩ፡፡ አባት አርበኛ በጋሻው ቴሶ ይባላሉ፡፡ በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ጊዜ የስምንት ዓመት ታዳጊ ነበሩ፡፡ በዚህ ዕድሜያቸው ጫካ ገብተው ነበር፡፡ ቀን ቀን ጫካ ውስጥ ተደብቀው በመዋል ማታ ማታ ወደቤት ይገባሉ፡፡ በዚህ ሁነት ውስጥ የነበረውን የውስጥ አርበኞችና የባንዳዎች ሁኔታ ያስታውሳሉ፡፡ ባንዳዎች እየሸሹ ሲሄዱ የጣሉትን መሣሪያም እያነሱ ይወስዱ ነበር፡፡
የውስጥ አርበኞች የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀሙ ነበር፡፡ የፋሽስት ጣሊያን ወራሪ እየመጣ ከሆነ ማሽላ ጠባቂ መስለው «ዝንጀሮ መጣ» እያሉ ይሰማማሉ፡፡ የዚህን ጊዜ አርበኞች ወራሪውን አዘናግተው ጥቃት ይፈጽሙ ነበር፡፡ በዚህ አጋጣሚም የወደቀ መሣሪያ ያገኙ ነበር፡፡ አባት አርበኛ በጋሻውም «እኔም አጭር ምንሽር የሚባል መሣሪያ ይዤ ነበር» በማለት ያስታውሳሉ፡፡ በወረራው ወቅት ሴት፣ ወንድ፣ ትልቅ፣ ትንሽ ሳይባል በዱር በገደል ተሰዶ ነበር፡፡ በአባቶች የተገኘውን ይህን ነፃነት ወጣቱ ትውልድ የመጠበቅ አደራ እንዳለበትም ያሳስባሉ፡፡
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በዝግጅቱ ላይ እንደተናገሩት፣ ማህበሩ ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን ይህን የድል በዓል በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አካባቢዎች እያከበረ ነው፡፡ ከማህበሩ ጋር የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ፣ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲና የከተማው አስተዳደር፣ በጎንደርና በትግራይ ዓድዋ ላይ ይከበራል፡፡ ይህ የድል በዓል በእነዚህ አካባቢዎች በሚቀጥሉት ቀናትም እንደሚከበር ነው የተናገሩት፡፡
ይህ የድል በዓል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው የጥቁር ሕዝብ ድል እንደሆነ ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት፡፡ ኢትዮጵያን አርአያ በማድረግ በርካታ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ ወጥተዋል፡፡ ይህም አገሪቱ የነፃነት አገር እየተባለች እንድትጠራ አስችሏል፡፡
በበዓሉ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንትና የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር የበላይ ጠባቂ ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የሚያዝያ 27 የድል በዓል ኢትዮ ጵያውያን በነፃነታቸው ላይ እንደማይደራደሩ ለጠላትም ለወዳጅም ያሳየ ነው፡፡ ጣሊያን በዓድዋ ላይ የደረሰበትን ሽንፈት ለማካካስ ለ40 ዓመታት ያህል ተዘጋጅቶ ቢመጣም ዳግም ኪሳራ አጋጥሞታል፡፡ ይህ የኢትዮጵያ የአሸናፊነት ወኔ ለአገሪቱ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ላሉ ቅኝ ተገዥዎች የነፃነት ምሳሌ የሆነ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የነፃነት ተምሳሌት መሆኗን ለማወቅ የሩቁ እንኳን ቀርቶ በቅርብ ዓመታት ሰላም ላጡ አፍሪካውያን አገሮች አለኝታ መሆኗ ምስክር እንደሚሆንና በኩራት እንድንናገር ያደረገን ይኸው የአገሪቱ አንድነትና ነፃነት እንደሆነ ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት፡፡ የአገሪቱን ሰላምና ነፃነት ለማረጋገጥ የተደረገው ጥረት አሁን ላይ የአገሪቱ ጠላት በሆነው ድህነት ላይ እንዲደገም አሳስበዋል፡፡
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ጥር 1 ቀን 1931 ዓ.ም ተጉለት «አንቀላፊ» በተባለ ቦታ ላይ በአፍላው ጦርነት ወቅት የተቋቋመ ሲሆን የወቅቱ የበላይ ሰብሳቢ ስመ ጥሩ አርበኛ ራስ አበበ አረጋይ ነበሩ፡፡ 

 

ዜና ሐተታ
ዋለልኝ አየለ

 

 

 

 

Published in የሀገር ውስጥ

የ2018ቱ የዓለም ዋንጫ ውድድር ሊጀመር ቀናቶች ቀርተውታል። አምስት ሳምንታት እና 39 ቀናቶች የቀሩት ይህ አጓጊ የዓለማችን ምርጥ የእግር ኳስ ስፖርት በሩሲያ አስተናጋጅነት የሚካሄድ ነው። በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ለአንድ ወር በዘለቀ የውድድር ቀናት አጓጊ ትዕይንቶች ይስተዋሉበታል ተብሎ ይጠበቃል። ያልተጠበቁ የእግር ኳስ ውጤቶች፣ ቀልብን የሚስቡ የደጋፊ ትዕይንቶች፣ ለጆሮ ያልተለመዱ፤ ለእይታ እንግዳ የሆኑ ወሬዎች እና ድርጊቶች በዚህ ውድድር ላይ እንደሚከሰቱ የሚጠበቅ ነው።
የዓለም ዋንጫን ከሌሎች ስፖርታዊ ውድድሮች ለየት የሚያደርገው የተለያየ ባህል፣ ቀለም እና ማንነት ያላቸው የስፖርቱ ቤተሰቦችን ከእግር ኳስ ውድድሩ በተጨማሪ በሌሎች ዝግጅቶች እና ትዕይንቶች ረዘም ለሚሉ ቀናት በበጎ ጎን ማስተሳሰር መቻሉ ነው። በዝግጅቱ ላይ ስፖርታዊ ወድድር ብቻ ሳይሆን የአዘጋጅ አገራት ባህል ይዳሰሳል። የቱሪዝም መስህቦች በታዳሚዎች ይጎበኛሉ። በዓለም ዋንጫው ላይ ከተለያዩ አገራት የመጡ ደጋፊዎች ድንበር የሚሻገር ጓደኝነት የሚፈጥሩበት፣ ከዚያም በዘለለ በጋብቻ የሚተሳሰሩበት አጋጣሚዎች ተፈጥረው ያውቃሉ። ለዚህም ነው ዓለም ዋንጫ ከእግር ኳስ ውድድር በላይ ፋይዳው ጉልህ እንደሆነ በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች የሚነገረው።
ስፖርት ወዳዱ ህብረተሰብ ከዓለም ዋንጫ አዘጋጅ አገራት አንድ ጉዳይ በተለየ መልኩ ይጠብቃል። የመክፈቻ ዝግጅት። ላለፉት ጊዜያት አገራት ውድድሩን ለማዘጋጀት ቃል ሲገቡ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ያለውን ድባብ ያማረ እና ስኬታማ ከማድረግ ባሻገር አንድ ቃል የሚገቡት ነገር አለ። ይኸውም የመክፈቻ ዝግጅቱን ከዚህ ቀደም ከነበሩት በተለየ መንገድ ደማቅ እና ልዩ ለማድረግ ከዓመት በላይ ዝግጅት ማድረግ ነው። በዚህ የመክፈቻ ዝግጅት ላይ አዘጋጇ አገር የደረሰችበትን የቴክኖሎጂ እና የኢኮኖሚ አቅም ለማሳየት ከመቻሏም በላይ ለስፖርታዊ ውድድሮች የምትሰጠውን ትኩረት አመላካች ይሆናል። በተለይም ባህል እና ወግ ብሎም አገራዊ ማንነት በመክፈቻ ዝግጅቶቹ ላይ ጎልተው እንዲታዩ ይደረጋል።
ስፖርት በተለይም እግር ኳስ የዓለምን ህዝብ እያዝናና አንድ የማድረግ ኃይል እንዳለው በተግባር የሚያሳዩ ትዕይንቶች ይቀርባሉ። እዚህ ጋር ነው እንግዲህ ሙዚቃ እና እግር ኳስ ዓለም ዋንጫ ላይ አንድ ሆነው የምናገኛቸው። በዛሬው የዕሁድ ስፖርት አምዳችን ላይ ስለ ዓለም ዋንጫ ዝግጅት ዳሰሳ እያደረግን ነው። ጥቂት ሳምንታት የቀሩት ይህ ተጠባቂ የእግር ኳስ ውድድር ተወዳጅ ጨዋታዎችን እና እልህ አስጨራሽ ፉክክሮች እንደሚከናወንበት ከወዲሁ ይገመታል። ሆኖም ለዛሬ በዝግጅታችን ለመቃኘት የፈለግነው ከውድድሩ ጎን ለጎን የሚካሄዱ እና የጨዋታው ድምቀት የሆኑ ሁነቶችን ነው። ይህን ስንል ደግሞ አንድ ጉዳይ በቶሎ በህሊናችን ላይ ይከሰታል፤ ሙዚቃ።
ስምንት ዓመታትን ወደኋላ መለስ ብለን የዓለም ዋንጫ ዝግጅት ስናስታውስ ደግሞ አፍሪካዊቷ «ደቡብ አፍሪካ» ያሰናዳችው የዓለም ዋንጫ በትዝታ መልክ ተቀምጦ እናገኘዋለን። ይህም ብቻ አይደለም የመሰናዶው ምልክት እና ማስታወሻ የሆነውን «ዋካ ዋካ» ወይም ይህ ጊዜ የአፍሪካ ነው የሚለው ማጀቢያ ዘፈን በቅድሚያ በትውስታችን ውስጥ መከሰቱ አይቀሬ ነው።
ሙዚቃ እና ስፖርት በተለይ በዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ውድድር ላይ መተሳሰር ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። ሁለቱ የመዝናኛ ዘርፎች ዓለምን አንድ የማድረግ ኃይል እንዳላቸው የተገነዘቡ ግለሰቦች እና ተቋማት በዝግጅቶቻቸው ላይ በጋብቻ እንዲተሳሰሩ በማድረግ ጣፋጭ ጊዜያትን ይፈጥራሉ። ለዚህም ነው መለስ ብለን የተለያዩ የውድድር ጊዜያቶችን ስናነሳ ታሪካዊ ዘፈኖች እና አርቲስቶችን የምናነሳው። እስቲ ለዛሬ ከዚህ ቀደም በዓለም ዋንጫ ዝግጅቶች ላይ የነበሩትን ማጀቢያ የሙዚቃ አልበሞች እና አርቲስቶች እያስታወስን በሩሲያው ውድድር ላይ ምን እንጠብቅ የሚለውን እንመልከት።
ሁለት አስርት ዓመታት መለስ ብለን የዓለም ዋንጫ ዝግጀትን እናስታውስ። 16ኛውን የዓለም ዋንጫ በአገሯ በማሰናዳት በእግር ኳስ ችሎታ ጫፍ ደርሶ የነበረውን የብራዚል ብሄራዊ ቡድን 3ለ0 በሆነ ውጤት በፍፃሜው ጨዋታ በመርታት ፈረንሳይ ዋንጫውን ማንሳቷ ይታወሳል። ይህን የውድድር ዘመን ደግሞ በስርቅርቅ ድምፃቸው መቼም እንዳይዘነጋ በማድረግ ያዜሙ ሙዚቀኞች ነበሩ። ከእነዚህ መካከል በ1990ዎቹ በዓለም ላይ ትልቅ ስም እና ዝናን አትርፎ የነበረው ፖርቶሪካዊው አርቲስት «ሪኪ ማርቲንስ» አንዱ ነበር። ይህ አቀንቃኝ የወቅቱን ዋንጫ ይፋዊ የሙዚቃ አጃቢ ነበር። የ1998ቱን ውድድር እና የብራዚልን ያልተጠበቀ ውጤት የሚያስታውስ ማንም የስፖርት ቤተሰብ « The Cup of Life» ወይም የህይወት ዋንጫ በማለት ያቀነቀነውን ተወዳጅ ማጀቢያ ሊዘነጋ አይችልም። ውድድሩን ከተለያየ ክፍለ አገራት ለመከታተል በፈረንሳይ ከትሞ የነበረው የስፖርት ቤተሰብም በዚህ ሙዚቃ አንድ ወር ከመዝናናቱም ባለፈ የስፖርትን እና የሙዚቃን ትስስር በማይረሳ መንገድ ለትዝታው ቋት ገብይቶ ነበር።
እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ 2002 የተደረገው የዓለም ዋንጫ ደግሞ ወደ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ይወስደናል። ይህ የዓለም ዋንጫ በብዙ መንገድ ልዩ የሚያደርጉትን ታሪካዊ ክስተቶች አስተናግዷል። ከእነዚህ መካከል በኤሺያ አገራት ተዘጋጅቶ የማያውቀውን ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ያዘጋጁት። ከዚህም ሌላ ለ16ጊዜ የተደረጉት ውድድሮች የተዘጋጁት በአንድ ሉዓላዊ አገር ብቻ ነበር። ሆኖም 17ኛው የዓለም ዋንጫ በልዩ ሁኔታ በሁለት አገራት ጣምራ ሊዘጋጅ ችሏል። በዚህም የዓለም እግር ኳስ ማህበር «ፊፋ» ውድድሩን ሁለት ጎረቤት አገራት በጋራ ማሰናዳት እንደሚችሉ የሚያሳይ ልምድ አግኝቶበታል።
ሌላኛው ልዩ የሚያደርገው ጉዳይ ደግሞ ለዛሬ ርዕሰ ጉዳያችን ያደረግነው የዓለም ዋንጫ ማጀቢያ ሙዚቃ ነበር። በዚህ የዓለም ዋንጫ ዝግጅት በ2000ዎቹ በፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝነት ዝናን አትርፋ የነበረችው አናስታሲያ በረስት የጃፓኑን እና የደቡብ ኮሪያውን ውድድር ደማቅ አድርጋው ነበር። «ቡም» የሚል መጠሪያ የነበረው ይህ ማጀቢያ በእግር ኳስ አፍቃሪያን ዘንድ ተወዳጅነትን በማግኘቱ ከ«ቫንጀሊክ» መዝሙር ጋር በጋራ ሲዘመር እና ሲቀነቅን ቆይቷል። ተወዳጁ የእግር ኳስ ውድድርም በዝነኛ አቀንቃኞች እንዲታጀብ እና ባህል እንዲሆን ትልቅ አስተዋፅኦ ነበረው። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ የ2006ቱ የጀርመን የዓለም ዋንጫ ነው። በዚህ ዝግጅት ላይ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኞቹ ኢል ዲቮ እና ቶኒ ብራክስተን በማጀቢያነት ማቅረባቸው ሙዚቃ እና ዓለም ዋንጫ እንደማይነጣጠሉ ያመላከተ ነበር።
የ2010 የዓለም ዋንጫ በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት ከመካሄዱም በላይ በማጀቢያ ሙዚቃ የተለየ ትውስታ ኖሮት በደማቅ ሁኔታ አልፏል። ከተዘጋጁት የማጀቢያ ሙዚቃዎች ውስጥ ደግሞ የሻኪራ «ዋካ ዋካ» ሁሉንም የስፖርት ቤተሰብ ከማዝናናት ባለፈ «ጊዜው የአፍሪካ» ነው የሚል መልዕክት ያስተላለፈ ነበር። ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮችን በብዛት የማታዘጋጀው አፍሪካም በሻኪራ ዋካ ዋካ ለአንድ ወር ፈንጠዝያ ውስጥ ቆይታለች። ተወዳጇ አቀንቃኝም ከሌሎች ዘፋኞች በተለየ ለስፖርቱ በተለይ ለእግር ኳስ ቅርብ መሆኗን አሳይታበታለች። ሻኪራ የውድድሩን ዋንጫ መሳም ከቻለው የስፔን ብሔራዊ ቡድን የተከላካይ መስመር ተጫዋች ጄራርድ ፒኬ ጋር ትዳር መስርታ ልጆችን ማፍራት የቻለችበትን የፍቅር አጋጣሚ መሰረት ያስያዘችበት የዓለም ዋንጫ ሆኖም ይታወሳል።
በደቡበ አፍሪካ በተሰናዳው ተወዳጁ ውድድር ላይም ከቀድሞዎቹ ዝግጅቶች በተለየ ታዋቂ እና ስኬታማ አቀንቃኞች ተሳትፈው ነበር። በዚህ የፊፋ ይፋዊ አልበም ላይ ከኮሎምቢያዊቷ አርቲስት ሻኪራ ጋር ክላውዲያ ሊት፣ የአር ኤንድ ቢ አቀንቃኙ አር ኬሊ፣ የሂፕ ሆፕ ተጫዋቹ ፒት ቦል እንዲሁም ጃፓናዊቷ የዘፈን ደራሲ ሚሲያ በተባባሪነት ሠርተዋል። በፍፃሜው ጨዋታ ስፔን ኔዘርላንድን በመሀል ሜዳው ጥበበኛ አንድሬስ ኢኒዬሽታ የተጨማሪ ሰዓት ግብ 1ለ0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ዋንጫውን ስታነሳ ዓለም ደግሞ በተወዳጁ ሙዚቃ «ዋካ ዋካ» ጣፋጭ አንድ ወርን አጣጥሟል።
ሌላኛው እና ከእግር ኳስ የትውስታ መዝገብ ውስጥ የማይፋቀው የሙዚቃ አሻራ ሻኪራ ለ2014 የዓለም ዋንጫ ማጀቢያ የሙዚቃ ሥራዋን የለቀቀችው ነው። ይህ ሥራ ከሌሎቹ ሙዚቃዎች ለየት የሚያደርገው በቪዲዮ ክሊፑ ላይ ሊዮኔል ሜሲ፣ ጄራርድ ፒኬ እና ኔይማር ማሳተፉ ነው። እነዚህ ተወዳጅ የዓለማችን የእግር ኳስ ጥበበኞች ኮሎምቢያዊቷ የሙዚቃ ኮከብ ሻኪራ ለ2014 የዓለም ዋንጫ ማጀቢያ የሚሆን አዲስ የሙዚቃ ሥራ «ላ ላ ላ» በሚል መጠሪያ ይፋ ስታደርግ በጋራ ሠርተዋል።
በሙዚቃ ሥራው የቪዲዮ ክሊፕ የባርሴሎናውን ኮከብ ባለቤቷን ጄራርድ ፒኬን፣ ሊዮኔል ሜሲን፣ ኔይማር እና በዓለም ዋንጫ የማይሳተፈውን ኤሪክ አቢዳል ብሎም ልጇ ሚላንን በማሳተፏ የዝግጅቱ ድምቀት ነበር። በተጨማሪም አርጀንቲናዊው ሰርጂዮ አጉዌሮ፣ ራዳሜል ፋልካዎ ተሳትፈዋል። በውድደሩ ወቅትም የዓለማችን ታላላቅ የቴሌቪዥን እና የራዲዮ ጣቢያዎች በተደጋጋሚ ይህን ሙዚቃ ሲያጫውቱት ከርመዋል። ስፖርቱም በሙዚቃው ታጅቦ በድምቀት ተጠናቋል። ሙዚቃው የአዘጋጇ አገር ብራዚል የሳንባ የሙዚቃ ምት እንዲኖረው ብራዚላዊውን ካርሊኖሆ ብራውን በፊቸሪንግ ተሳትፎበት ነበር። በተለይ ሻኪራ በ2010 የዓለም ዋንጫ «ዋካ ዋካ» በሚል መጠሪያ የሠራችው የደቡብ አፍሪካ ዓለም ዋንጫ ማጀቢያ ሥራ በበርካቶች ዘንድ መወደዱ በዚህኛውም ሥራዋ ላይ በጉጉት እንድትጠበቅ አድርጓት ነበር። የሻኪራ «ላ ላ ላ» የተሰኘው ማጀቢያ የጄነፈር ሎፔዝና ፒት ቡል «ኦላ ኦላ» ጋር ተደምሮ ሙዚቃ በስፖርት ላይ ሞገስ እና ፍቅር እንደሚጨምር ማሳየት ችሏል።
ሩሲያ 2018
የፊፋ የዓለም ዋንጫ በሩሲያ አስተናጋጅነት በአውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር ከሰኔ 14 እስከ ሀምሌ 15 2018 እንዲካሄድ መርሐ ግብር ተይዞለታል። በጉጉት የሚጠበቀው ውድድር ሊጀመርም አምስት ሳምንታት ብቻ ቀርተውታል። ፊፋ ከውድደሩ ጅማሮ አስቀድሞ ለሦስት ጊዜያት የዓለም ዋንጫው በተመረጡ ሃገራት እንዲዘዋወሩ አድርጎ ነበር። በተመሳሳይ ለአራተኛ ጊዜ በበርካታ አገራት ዋንጫው ተዘዋውሯል። የፊታችን ግንቦት አንድም በሩሲያ ማጠናቀቂያውን ያደርጋል።
ፊፋ ዋንጫው እንዲጎበኛቸው የመረጣቸው አገራት 51 ሲሆኑ፤ 91 ከተሞች ላይ ተዟዙሯል። ይህ ዕድል ለኢትዮጵያም ደርሷታል። ከኢትዮጵያ ቀጥሎ ዕድሉ ለኬንያ ሲደርሳት በ36 ከተሞች በአድናቂዎቹ አቀባበል ተደርጎለታል። የዓለም ዋንጫም ከስፖርቶች ሁሉ በስፋት ተወዳጅነትን ያተረፈ ለመሆን በቅቷል። ለዚህም ነው ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በሚጀመረው የሩሲያው ዝግጀት ላይ የሚቀርቡ ዓለም አቀፍ ሙዚቃዎች በተመሳሳይ በጉጉት የሚጠበቁት። እውቅ አቀንቃኞቹ ሻኪራ፣ አናስታሲያ፣ ሪኪ ማርቲን ላለፉት ጊዜያት ዓለም ዋንጫን በዜማ አድምቀዋል። አሁን በ2018ቱ የሩሲያ ዝግጅት የትኛው ዘፈን ተወዳጅ ይሆናል የሚለው ጥያቄ ደግሞ እልህ አስጨራሽ ከሆነው የብሄራዊ ቡድኖች ፍትጊያ ውጪ ተጨማሪ ጉጉትን ፈጥሯል።
በርከት ያሉ የማስታወቂያ ድርጅቶች ከወዲሁ የዓለም ዋንጫን መምጣት እያበሰሩን ይገኛሉ። ልክ እንደ አዲስ ዓመት መባቻ ሁሉ ለዚህ ውድድርም ከወዲሁ «እንኳን አደረሳችሁ» የሚል መልዕክት በእነዚህ የማስታወቂያ ድርጅቶች እና የመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ለስፖርት ቤተሰቡ እየተላለፈ ይገኛል። ሆኖም በዓሉን እነዚህ ማስታወቂያዎች ብቻ አይደሉም የሚያደምቁት። ላለፉት ዓመታት ስፖርቱ ደማቅ እንዲሆን በማድረጉ ረገድ ቀዳሚውን ድርሻ የሚወስዱት ተወዳጅ አቀንቃኞች ጭምር ናቸው።
የዓለም እግር ኳስ ማህበሩ «ፊፋ» እና አጋር ደርጅቶቹ እግር ኳሱ ያለ ተወዳጅ ሙዚቃ ደማቅ እንደማይሆን ያለፈው ልምዳቸው ስላስገነዘባቸው ጥሩ የሚባል የማይዘነጋ ትዝታን ለመጣል ከወዲሁ እየተሯሯጡ ይገኛሉ። ሙዚቃውን ሲሰሙ የዓለም ዋንጫን፤ የዓለም ዋንጫን ሲያስቡ ተወዳጁን ሙዚቃ በጭንቅላታቸው የሚያሰላስሉ የእግር ኳስ ወዳጆችም ጉዳዩን በትኩረት እየጠበቁ ናቸው። በዚህም የተለያዩ አቀንቃኞች ከወዲሁ ተወዳጅ ሙዚቃ እና ይፋዊ የዓለም ዋንጫ መዝሙራቸው ተቀባይነት እንደሚያገኝ ተገምቷል።
ጄሰን ዱሩሎ
አሜሪካዊው ተወዳጅ አቀንቃኝ እና የዘፈን ደራሲ ጄሰን ዱሩሎ በሩሲያው የዓለም ዋንጫው ላይ ድምቀት ሆኖ ብቅ ያለ አቀንቃኝ ነው። «ከለር» የተሰኘው ሙዚቃው በኮካኮላ የዓለም ዋንጫ ማጀቢያ እንዲሆን ተመርጧል። ይህ ሙዚቃ አብሮነት እና ከዘረኝነት የፀዳ አዲስ ዓለም ምን ያህል ውብ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። ሙዚቃው በጉጉት ለሚጠበቀው ዓለም ዋንጫም ልዩ ምልክት እንደሚሆን እየተጠበቀ ነው። የማህበራዊ ድረ ገፅ በሆነው የምስል ማጋሪያ «ዩቱይብ» ከ14 ሚሊዮን ሰዎች በላይ ተመልክተውታል።
ጄሰን ዱሩሎ መጋቢት 9 «ከለር» የተሰኘውን ዘፈን ለዓለም ዋንጫ መልቀቁን ተከትሎ በቲውተር ገፁ «ሁላችሁም አገራችሁን ወክሉ፤ ባንዲራችሁን ወክሉ፤ በመጣችሁበት እና ባላችሁ ማንነት ኩሩ» በማለት ዘፈኑን በይፋ ለውድድሩ መልቀቁን አስታውቆ ነበር።
ጥቂት ስለ ዓለም ዋንጫ ታሪክ
ጊዜው እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር 1930 ነው። እግር ኳስን በበላይነት ለመምራት እና ተወዳጅነቱን ለማስፋት ጉልህ ሚናን የተጫወተው የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር «ፊፋ» በታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የዋንጫ ውድድር ያደረገው። የያኔው የፊፋ ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ሪሜት እግር ኳስን በዓለም ዋንጫን ማዕቀፍ ስር በማድረግ ከኦሎምፒክ ስፖርቶች ነጥሎ ለማድረግ የተገደደበት አንድ አጋጣሚ ነበር።
የኦሎምፒክ ስፖርት አዘጋጆች በ1932 በአሜሪካ ሎስአንጀለስ በሚካሄደው ውድድር ላይ ከስፖርታዊ ክንውኖች መካከል እግር ኳስን ለማካተት ፍላጎት በማጣታቸው ማህበሩ ለብቻው ተገንጥሎ የራሱን ውድድር ለማድረግ ውሳኔ አሳለፈ። ይሄ አጋጣሚ እግር ኳስ ዓለም አቀፍ ተወዳጅነትን እንዲያተርፍ የዕድል በሩን ከፈተ እንጂ ጭርሱኑ እንዲጠፋ አላደረገውም።
በመጀመሪያው የዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ 13 አገራት ብቻ ተሳትፈዋል። ውድድሩ አሀዱ ብሎ ሲጀምር አሁን የደረሰበት የተወዳጅነት ልክ ላይ ይደርሳል የሚል ግምት አልነበረም። ለዚህም ነበር ከጅምሩ 13 አገራትን ሊያውም 7ቱ ከአዘጋጅ አገሯ ከኡራጋይ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙት የደቡብ አሜሪካ አገራት የተሳተፉበት። የእግር ኳስ ማህበሩ አባላቱን በተለይም አውሮፓውያኑ ቡድናቸውን ወደ ኡራጋይ ልከው ውድድር እንዲያካሄድ አድርጎ ነበር። ሆኖም እውሮፓውያኑ አትላንቲክ ኦሽንን አቋርጦ በደቡብ አሜሪካዋ አገር ላይ ውድድሩን ማድረግ ከርቀቱና ከሚያስወጣቸው ከፍተኛ ወጪ አኳያ ሊቀበሉት አልቻሉም ነበር። በዚህ የተነሳም 13 አገራት ብቻ ተሳታፊ ሆነዋል። ከዚያ ዘመን አንስቶ ውድድሩ በዕድገቱ በርካታ ስኬቶችን እያስመዘገበ መርሀ ግብሮቹን እያሰፋ እና ተወዳዳሪ አገራትን እየጨመረ መጥቷል። በዚህም አሁን 32 አገራት ተሳታፊ ሲሆኑ፤ 200 የሚሆኑት ደግሞ ሁለት ዓመት በሚፈጀው የማጣሪያ ውድድር ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ።
ጥቂት ስለ መወዳደሪያ ስታዲዮሞች
በታኅሣሥ መጀመሪያ በሞስኮ በወጣው የምድብ ድልድል በወርሀ ሰኔ ጅማሮውን ለሚደረገው የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ አገራት የምድብ ተጋጣሚዎቻቸውን አውቀዋል። በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ለወራት ተፋልመው ለታላቁ ውድድር የተሳታፉ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ታዲያ ሩሲያም እንግዶቿን ተቀብላ በስኬት ውድድሮችን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ማድረጓን በተለያዩ የመገናኛዎች ሲዘገብ ቆይቷል። ዝግጅቱን በዋናነት ያደምቁታል ተብለው የሚጠበቁት ደግሞ አዳዲስ እና በጥሩ ሁኔታ በድጋሚ የታደሱት ስታዲየሞቿ ናቸው። አገሪቷ32ቱ ቡድኖች ሰላማዊ ፍልሚያ ያደርጉበታል ያለቻቸውን 13 ስታዲየሞች ይፋ አድርጋለች። ከዚህ ቀደም በስፋት ስለስታዲዮሞቹ የነገርናችሁ ቢሆንም በጥቂቱ እናስታውሳችሁ።
«ሉዙኒኪ ስታዲየም» በሩሲያ ግዙፉ ስታዲየም ነው። በዋና ከተማዋ ሞስኮ ይገኛል። 81ሺ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም አለው። «ኦቲሪቲ አሬና» ይህ ስታዲየም እንደ ሉዚኒኪ ስታዲዮም በሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ ውስጥ ይገኛል። የፍፃሜ ጨዋታ ከሚያስተናግደው ዋናው ስታዲየም በግማሽ ያህል ቀንሶ 45ሺ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም እንዲኖረው ተደርጎ ተገንብቷል። «ካዛን አሬና» በካዛን ከተማ ውስጥ ይገኛል። 45 ሺ 379 ተመልካቾችን የመያዝ አቅም አለው። ታዋቂው የሩሲያ እግር ኳስ ክለብ ሮቢን ካዛን ንብረት ነው። በዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን እንዲያስተናግዱ ከተመረጡ ውስጥ በሦስተኝነት ተካቷል።
ከላይ በጥቂቱ ያነሳንላችሁ ስታዲዮሞች በተወዳጅ እና ታዋቂ ሙዚቀኞች፤ የአገራቸውን ብሄራዊ መዝሙር በሚያቀነቅኑ ውብ ደጋፊዎች ደምቀው ይሰነብታሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን በሩሲያ የሚካሄደውን «ታላቁን ዋንጫ» ማን ያነሳው ይሆን? ጥያቄ ከሁሉም ነገር በላይ ገዝፎ በእግር ኳስ አፍቃሪዎች መካከል ጥያቄ ሆኖ ይቆያል። ዓለም ዋንጫ 5 ሳምንታት ቀርተውታል።

ዳግም ከበደ

Published in ስፖርት

እኔ እምለው ግን በዚህ ነገር ያልተማረረ ይኖር ይሆን? ማለቴ በጩኸት፡፡ ወይስ እኔን ብቻ ነው እንዲህ ያስመረረኝ? በቃ አዲስ አበባ ውስጥ እኮ ሰው ሰራሽ በሽታዎች በዙብን፡፡ በሳይንስ የሚታወቀው ተላላፊ በሽታ፣ የማይተላለፍ በሽታ፣ በምንድንትስ የሚተላፍ በሽታ እየተባለ ነበር፡፡ አሁን ግን ‹‹ሰው ሰራሽ በሽታዎች›› የሚባል በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ መካተት አለበት፡፡ ለምሳሌ በቆሻሻ ምክንያት መታመም ሰው ሰራሽ እኮ ነው፡፡ ራሳችን በደፋነው ቆሻሻ ነው፤ የጆሮ ታምቡር የሚበጥስ ሙዚቃም ቢሆን ሰው ሰራሽ ነው፤ የመኪና ክላክስ ሰው ሰራሽ ነው፡፡ ለማንኛውም ሳይንሳዊ ብያኔው ይቅርብኝና የጩኸት ነገር ግን በጣም እያሰጋኝ ነው፡፡
ሁሉም ነገር አስፈላጊ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ሙዚቃ አስፈላጊ ነው፤ መዝናኛ ነው፣ መደሰቻ ነው፣ መልዕክት ያስተላልፋል። ይህን ሁሉ የምናጣጥመው ግን ሙዚቃ ሲሆን ነው እንጂ ጩኸት ሲሆን አይደለም፡፡ በሞንታርቦ የተለቀቀ ሙዚቃ እኔ ምኑም አይጥመኝም፡፡ አንዳንድ ጊዜ እኮ እስከላንቃው ከመለቀቁ የተነሳ ሲጥጥጥ የሚል ድምጽ ነው የሚያወጣው፡፡ እንኳን ዘፈኑን ማዳመጥ የማን ዘፈን እንደሆነ እንኳን መለየት እስከሚያስቸግር ይጮሃል፡፡ በዚያ ውስጥ ከሚዝናናው ይልቅ ጆሮውን ይዞ ፊቱን የጨፈገገው ሰው ይበዛል።
ሌላው ደግሞ የሚገርመው በአንድ አካባቢ የተደረደሩ የንግድ ቤቶች ውስጥ ሁሉም ሙዚቃ መልቀቃቸው ነው፡፡ እዚያ አካባቢ የየትኛውም ሙዚቃ ይረብሻል እንጂ አይደመጥም፡፡ ከየስፒከሩ የሚወጣው ድምጽ ተዳምሮ አካባቢውን ጦርነት የተፈጠረበት ሜዳ ያስመስለዋል። ይሄ እንግዲህ ለመረበሽ ካልሆነ በስተቀር ማን የማንን ሙዚቃ እያጣጣመ ይሰማል?
አዲስ አበባ ውስጥ እኮ ስልክ ማውራት እንኳን አልተቻለም፡፡ ጩኸት ያለበትን ቦታ አልፌ ሌላ ቦታ ሄድኩ ስትል የባሰ ያጋጥምሃል፡፡ ከዚያ በኋላ ‹‹ምን አልከኝ፣ ምን አልሽኝ›› እያልክ መጮኸ ነው፡፡ እዚህ ላይ ግን ሚስት ላላቸው ሰዎች አዘንኩ፡፡ በስልኩ ውስጥ ድብልቅልቅ ያለ ሙዚቃ የሰማች ሚስት ጭፈራ ቤት መስሏት ‹‹እየመጣሁ ነው ብለህ ትጨፍርልኛለህ አይደል?›› ልትል ትችላለች፡፡ እሱ እንደሆነ እንኳን ሊጨፍር የታክሲ ሰልፍ እርግጫ እየጨፈረበት ነው (እንዲህ በግምት እኮ ትዳር ፈርሶ ይሆናል)፡፡
የስልክን ነገር ካነሳን አይቀር ግን ከእኔ አንድ ተሞክሮ ላካፍላችሁ፡፡ በጣም ጩኸት የበዛበት ቦታ ስትሆኑ አጭር የጽሑፍ መልዕክት መጠቀም ነው፡፡ ሰው ግን ለምንድነው የሚነበብ ነገር አይወድም? በአጭር የጽሑፍ መልዕክት እኮ ብዙም የሚጠቀም የለም፡፡ እኔ ብዙ ጊዜ ጽፌ ‹‹አላየሁትም›› ነው የሚሉኝ፡፡ ምናልባት ይሄ ሰማንያ ምናምን ቤት አሰልችቷቸው ይሆናል፡፡ ቢሆንም ግን ምንም ሆነ ምን ወደ ስልካችን የገባ መልዕክትን እኮ ማየት አለብን፡፡ የተደበላለቀ ጩኸት ውስጥ ሆኖ ‹‹ምን አልክ›› እያሉ ከመጯጯህስ አጭር ጽሑፍ መፃፍ አይቀልም?
እስኪ ወደ ጩኸታችን እንመለስ፡፡ እንግዲህ መንገድ ለመንገድ እየሄድን ይህን ያህል ጩኸት ካጋጠመን ካፌ ወይም ምግብ ቤትና መጠጥ ቤት ገብተን ደግሞ ምን እንደሚያጋጥመን አስቡት፡፡ ሙዚቃ እኮ መከፈት ያለበት ቢያንስ ማታ ማታ ነው፡፡ እሺ ቀንም ይሁን ከተባለ ለመስማት እስከሚያስቸግር ባይጮኸ ምን ችግር አለው? ሰው እኮ ወደ ካፌና ሬስቶራንት የሚገባው የመጠጥ ሱስ ኖሮበት ብቻ አይደለም፤ ከቤቱ የሚበላ አጥቶ አይደለም፡፡ ካፌ ውስጥ የሚገባው ለጨዋታም ጭምር ነው፡፡ በተለይ አዲስ አበባ ውስጥ ደግሞ አስቡት፤ ሰው ከሰው ጋር ሲገናኝ ያለው አማራጭ የሆነ ቤት መግባት ነው፡፡ ዛፍ ሥር ቁጭ ብለው ይጫወታሉ አይባል ዛፍ የለ፤ ወንዝ ዳር ቁጭ ብለው ይጫወታሉ አይባል የአዲስ አበባ ወንዞች እንኳን ቁጭ ብሎ ለመጫወት ለማለፍ እንኳን አፍንጫን ይዞ እየሮጡ ነው፡፡
ለጨዋታ ብሎ የገባ ሰው መሰማማት እስከሚከለክል የሙዚቃ ጩኸት ይለቀቅበታል። ጉሮሮህ እስከሚደርቅ የቻልከውን ያህል እየጮኸክ ታወራለህ፡፡ ከዚህ ያለፈ አስቸጋሪ ከሆነ ያለው አማራጭ መውጣት ብቻ ነው፡፡ ዕውነት ግን ያ ሁሉ ጩኽት ለደንበኞች ፍላጎት ተብሎ ነው? ማንም የሚፈልገው ደንበኛ እኮ የለም፡፡ ሙዚቃ የሚፈለግበት ሰዓትና ሁኔታ አለው፡፡ ለምሳሌ የበዓል ሰሞን ከሆነ ይፈለጋል፣ ማታ ማታ ይፈለጋል (ለዚያውም መጠጥ ቤት ከሆነ)፤ የተያዘው ቤት ለሆነ ዝግጅት በኪራይ ከሆነ ባለዝግጅቶቹ እንደፍላጎታቸው ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ ከዚያ ውጭ ግን ገና ከማለዳው በጩኸት ማደበላለቅ የደንበኛ እርካታ አይደለም፡፡
ሌላው የሰለቸኝ ጩኸት ደግሞ የታክሲ ውስጥ ሙዚቃ ነው፡፡ አስቡት ታክሲ ደግሞ ጠባብ ናት፡፡ እዚያው ውስጥ እስፒከሩ ሊሰነጠቅ የደረሰ እስከሚመስል ድረስ ይለቀቃል፡፡ ብዙ ጊዜ ደግሞ የምሰማው የእንግሊዘኛ ዘፈንና ሬዲዮ ከሆነ ደግሞ የስፖርት ፕሮግራም ነው፡፡ ያንን እያጮኸ ሾፌሩ ‹‹ወራጅ አለ›› ሲባል እንኳን አይሰማም፡፡ ረዳቱ አይሰማ፣ ሾፌሩ አይሰማ! ረዳቱ ከአጠገብህ ስለሚሆን ጎስመህም ቢሆን ልታናግረው ትችላለህ፤ ረዳቱ ለሾፌሩ ወራጅ አለ ሲለው አይሰማም (ስልክ ካልደወለለት በስተቀር) በዚህ መጯጯህ መሃል የምትወርድበትን ቦታ አልፈኸው እንደገና በታክሲ ልትመለስ ትችላለህ፡፡
የሾፌሮች ነገር ከተነሳስ ሌላም የባሰ ችግር አለባቸው፡፡ ቆይ ግን የመኪና ክላክስ ህግ የለውም? በአንድ የሬዲዮ ጣቢያ ላይ አንድ የህግ ባለሙያ ሲያወራ እንደሰማሁት ክላክስ ለማጮኸ የራሱ የሆነ ህግና ደንብ አለው፡፡ ያንን የተላለፈም ይቀጣል፡፡ ይህን ነገር ግን ማንም ሾፌር የሚያውቀው አይመስልም፡፡ አልፈርድባቸውም በዚህ ተቀጥቶ የሚያውቅም የለማ። አንዳንዶቹ እንዲያውም እንደ መጫወቻ የሚጠቀሙት ሁሉ ይመስለኛል፡፡ ከፊቱ ምንም ነገር ሳይኖር ጭርርርር አድርጎ ያጮሃል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከፊቱ ያለው መኪና ማለፊያ አጥቶ እንደቆመ እያወቀ ያለማቋረጥ ለረጅም ጊዜ ያጭሃል፡፡ መሄድ እንደማይችል እኮ ያውቀዋል፡፡ እሱ ከውስጥ ስለሆነ አይረብሸው ይሆናል፤ ከመንገድ ዳር ያለ ሰው እኮ በጣም እየተረበሸ ነው። እንዲያውም ከጩኸቶች ሁሉ የመኪና ጩኸት የበለጠ ይረብሻል፡፡
በነገራችን ላይ የድምጽ ብክለት ከባድ አደጋ እንዳለው የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ ዳሩ ግን ስለድምጽ ብክለት ምንም ሲባል አይሰማም፡፡ የድምጽ ብክለት እንደ ችግር ሲቆጠር አይስተዋልም፡፡ ምናልባት በአይን የሚታይ ውጫዊ አደጋ ስለሌለው ይሆናል፡፡ ጆሮ ተጎዳ ማለት ግን ቀላል ጉዳት አይደለም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ግን የሚቆጣጠር አካል የለም? እስካሁን ከሌለ እንኳን ቢያንስ ለወደፊቱ መኖር አለበትና የሚመለከታችሁ አካላት እዩን። ኧረ የጩኸትን ነገር እናስብበት!!

ዋለልኝ አየለ

Published in መዝናኛ

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ባህሎችን ልብ ብንል ጀግንነት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ እንዳለው እንረዳለን፡፡ ከጥንታዊው የአደን ሕይወት ጀምሮ ዛሬ ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ጀግንነት ከባህል ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ከዘመን ዘመን የተለያየ ቢሆንም ዛሬም ድረስ ጀግንነት ትልቅ ዋጋ ይሰጠዋል። ለምሳሌ በቀድሞው ጊዜ ‹‹አንበሳ ገዳይ፣ ነብር ገዳይ›› እየተባለ ይሞገስ ነበር፡፡ አነጣጥሮ ዒላማውን የሚመታ ሰው ‹‹ተኳሽ›› እየተባለም ይሞካሻል።
እንደየዘመኑ የተለያየ መሆኑን የምናውቀው ደግሞ አሁን ላይ በምናየው የጀግንነት ትርጉም ነው፡፡ ለምሳሌ በገጠር አካባቢ አንድ አርሶ አደር ለእርሻ አስቸጋሪ የሆነን ማሳ አለስልሶት ከታየ ‹‹እገሌ እኮ ጀግና ነው አፈሩን ገራው» ይባላል፡፡ በዝናብ ሰብል ሲያርም የታየን ሰው ደግሞ ‹‹አይ ጀግንነት አይበገሬው›› እየተባለ ሲሞገስ ይሰማል፡፡ በትምህርት ቤት እንኳን ብንሄድ አንደኛ የሚወጣ ተማሪ ‹‹የእገሌ ልጅ ጀግና እኮ ነው›› ይባልለታል፤ በጓደኞቹ ዘንድም ትልቅ ክብር ይሰጠዋል፡፡
ሌላው ጀግንነት በኢትዮጵያ ውስጥ ባህል መሆኑን የምናውቀው በሰርግ እና በሌሎች የድግስ ጉዳዮች ላይ ሲጫወቱ የሚወዳደሱት ጀግንነትን መሰረት በማድረግ ነው፡፡ የድሮ አባቶችን ገድል መዘከር ብቻ ሳይሆን የአሁን ልጅም ጀግና መሆን እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አባቴ ጀግና ነበር ማለት ብቻ ሳይሆን ራሱ ሰርቶ ማሳየት እንዳለበት ለመጠቆምም እንዲህ እየተባለ ይዘፈናል፡፡
አርገው ሞቅ ሞቅ እንደ ደሬ ፍም
የአባት ጀግንነት ለልጅ አያልፍም!
ደሬ ማለት የዛፍ አይነት ሲሆን፤ ሲደርቅ ማገዶ ይሆናል። የደሬ እንጨት ፍሙ ቶሎ አይጠፋም። ለዚህም ነው ደሬ የተባለውን እንጨት የመረጡት። የእረኞችን ጨዋታ እንኳን ብናስተውል በማሸነፍና በመሸነፍ ላይ የተመሰረተ ነው። ድንጋይ በማቆም ዒላማ መሳት አይቻልም። ስለዚህም የዘወትር ጨዋታቸው ይህንን የያዘ ነው። ከርቀት ሆኖ የቆመውን ድንጋይ በተወርዋሪ ድንጋይ መምታት የጀግንነት ምልክት ነው። እረኞች ከኮባ ወይም ከሸንበቆ የተዘጋጀ ጠመንጃ መሰል ነገር መያዝ ይወዳሉ። ይሄ እንግዲህ ከአካባቢያቸው ሁኔታ ተነስተው የሚያደርጉት የጀግንነት ልምምድ ነው። አሁን ደግሞ ድህነትን መርታት ጀግንነት የሆነበት ዘመን ላይ ደርሰናል።
ጀግንነት ጥበብ ነው። በጦርነት ታሪክ ውስጥ በተለይም ኢትዮጵያውያን በጥበብ እንደሚያሸንፉ በብዙ የታሪክ ጸሐፍት ተጽፏል። ታላቁን የዓድዋ ድል እንኳን ብንወስድ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀው የጣሊያን ሰራዊት በጦር፣ በጎራዴና በኋላቀር መሳሪያ በታጠቁ ጀግኖች ነው ዓለም አቀፍ ውርደትን የተከናነበው። ለዚህም ኢትዮጵያውያን አርበኞች የተጠቀሙት የተለያየ ጥበብ እንዳለ መረዳት ይቻላል። ትናንት በተከበረው የአርበኞች ድል ቀንን አስታከን እንኳን ብዙ ጥበብ የተሞላባቸው አሸናፊነቶችን መጥቀስ እንችላለን። ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983›› በሚለው በታሪክ ተመራማሪው ባህሩ ዘውዴ መጽሐፍ ላይ ተጽፎ እንደምናገኘው ራስ አበበ አረጋይ ይህን ስልት ተጠቅመው ነበር።

አባት እና እናት አርበኞች፤


በ1932 ዓ.ም ራስ አበበ አረጋይ ለጣሊያን ‹‹እጄን ሰጥቻለሁ›› በማለት አጃጅሏቸው ነበር። ይህ መጭበርበር የደረሰበትም ምክትል እንደራሴና የሸዋ ገዥ የነበረው ጄኔራል ናዚ ነበር፡፡ ራስ አበበ አረጋይ ለናዚ ‹‹እጄን ሰጥቻለሁ›› በማለት ለአርበኞች ጓደኞቹ ‹‹አይዟችሁ እንዲህ እያልኩ እያታለልኳቸው ነው›› እያለ ይልክባቸው ነበር፡፡ ናዚም ምንም ሳይጠረጥር እውነት መስሎት የሰላም ድርድሩን ተያያዘው፡፡ በኋላም ራስ አበበ አረጋይ ጦሩ ቀደም ሲል የደረሰበትን ጥቃት ማገገሙን ሲያረጋግጥ ጣሊያንን ‹‹ዞር በል!›› በማለት ትግሉን ቀጠለ።
ሌላኛው የጦርነት ስልታቸው ደግሞ በወቅቱ የማይጠረጠሩትን ሴቶችን ማሰለፍ ነበር፡፡ ለዚህም እነ ሸዋረገድ ገድሌና አርበኛ ከበደች ሥዩም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በዓድዋው ጦርነትም የእቴጌ ጣይቱን ጥበብ ተዳጋግሞ መጠቀሱን ልብ ይሏል፡፡ የጣሊያን ምርኮኛ መስለው የሰራዊቱን ጥንካሬና ድክመት ያጠኑ የነበሩ ሰላዮችም ነበሩ።
በሌላ በኩል ደግሞ በተለያየ መንገድ ያታልሏቸው ነበር፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያውያን በባዶ እግራቸው የሚሄዱም ስለነበሩ የእግራችን ዳና እየተከተለ ጠላት ያጠቃናል ብለው የጠረጠሩ አርበኞች አንድ ዘዴ ፈጠሩ፡፡ ለምሳሌ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ መሄድ ፈልገው ከሆነ የእግር ዳና በመፍጠር ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ ይሄዳሉ፡፡ ከዚያም የእግር ዳና ሳይፈጥሩ ወደ ምዕራብ ይመለሳሉ፡፡ ጠላት ወደዚያ ሄደዋል ብሎ በተቃራኒ አቅጣጫ ሲነጉድ ከኋላ ያጠቁት ነበር፡፡
ይህ እንግዲህ ተጽፎ ያገኘነውና ሲባል የሰማነው ነው፡፡ ያልተጻፈና ሲባልም ያልሰማነው ደግሞ ብዙ ስልት ተጠቅመዋል፡፡ ለዚህም ምስክር የሚሆነው ኃያላን ከሚባሉ አገራት የመጣውንና ዘመናዊ መሳሪያ እስከአፍንጫው የታጠቀውን ወራሪ ድል ማድረጋቸው ነው፡፡ ጥበባቸው ኢትዮጵያውያን አርበኞች አገሪቱን በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ብቸኛ አገር ተብላ በታሪክ መዝገብ ላይ እንዲትሰፍር አደረጓት።
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የጀግንነትን ነገር እናንሳ ከተባለ እያንዳንዷ ዕለት ጀብዱ የተፈጸመባት ትሆናለች። ዳሩ ግን ሦስት ቀኖች ደግሞ በተለየ መልኩ ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው ናቸው። የካቲት 12፣ የካቲት 23 እና ሚያዚያ 27 በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ ይሰጣቸዋል። የካቲት 12 ግፈኛው ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵ ያውያንን የጨፈጨፈበት ሲሆን፤ የካቲት 23 የአድዋ ድል እና ሚያዚያ 27 የድል ቀን ናቸው። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያላቸው እነዚህ ሦስት ቀናት ሁሉም ከጣሊያን ወራሪ ጋር ይያያዛሉ። የተክለ ጻድቅ መኩሪያ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ሃይለ ሥላሴ›› የባህሩ ዘውዴ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983›› መጻሕፍት እና ልዩ ልዩ ድረ ገጾችን ዋቢ አድርገን የአርበኞችንን ምንነት እናስታውስ፡፡
ጣሊያን በ1888 ዓ.ም ዓድዋ ላይ ዓለም አቀፍ ውርደት ተቀበለ። ከዚያ የአንድ ጎልማሳ ሰው ዕድሜ ያህል ሽንፈቱ ውስጡን ሲከነክነው ኖረ። ቂሙን ሊወጣ ዳግም በንጉሱ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ መጣ (ኢትዮጵያውያን ግን አሁንም ጀግኖች ነበሩ)። ኢትዮጵያንም በግፍ ወሮ ያዘ። በታሪካዊው ቀን የካቲት 12/1929 ዓ.ም የኔፕልስ ልዕልት በመወለዷ ግራዚያኒ የደስታ መግለጫ ገንዘብ እሰጣለሁ ብሎ ከዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከድሮው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ቤተመንግስት ሰዎች እንዲሰበሰቡ አዘዘ።
ታላላቅ የጣልያን ሹማምንት፣ የሜትሮፖሊታን ጳጳስ አቡነ ኪርልና ሌሎችም በቦታው ነበሩ። ለእያንዳንዱ ሰው ሁለት ማርትሬዛ ብር እንዲሰጥ ተወስኖ ነበር። ይህ ልኩን ያለፈ የጣሊያን አገዛዝ ያንገበገባቸው ሞገስ አስገዶምና አብርሃም ደቦጭ የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው ወደ አዳራሹ ገብተው ነበር። ጀግኖቹ ያሰቡትን አደረጉ። ግራዚያኒ ላይ ቦንብ ተወረወረ። ድግሱ ወደ ጦርነት ተቀየረ። በዚህ ሰበብም ጣሊያን የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ህይወት ቀጠፈ። ከዚያ በኋላ እንግዲህ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች በዱር በገደል ተሰደዱ። በከፍተኛ መስዋዕት ግፈኛውን የጣሊያን ወራሪ በተለያየ ስልት ሲዋጉ ቆይተው በ1933 ዓ.ም ሚያዚያ 27 የድል ቀን ሆነ።
በጣሊያን የወረራ ዘመን ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማዋ ከታጠፈ፣ ሉዓላዊነቷ ከተደፈረ 5 ዓመታት በኋላ ነፃነቷን ያስመለሰችው ከ77 ዓመት በፊት ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በ11 ሰዓት ንጉሰ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በአርበኞች ብርታትና መስዋዕትነት የጣሊያን ባንዲራ አውርደው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በታላቁ ቤተ-መንግሥት በሰቀሉበት ወቅት ነበር። የሚያዝያ 27 የንጉሰ ነገስቱ አዲስ አበባ ገብቶ ሰንደቅ ዓለማ መስቀል ሌላው ታሪካዊነቱ ከአምስት ዓመታት አስቀድሞ ሚያዝያ 27 ቀን 1928 በዚያው ቀን ወደ ኢትዮጵያ የዘመተው የጣልያኑ ጦር አዛዥ ጄኔራል ባዶሊዩ አዲስ አበባ ገብቶ በታላቁ ቤተ መንግሥት የጣሊያንን ባንዲራ የሰቀለበት ቀን መሆኑ ነው።
ጣሊያን ከዓድዋ ሽንፈቷ 40 ዓመታት በኋላ በዘመናዊ የጦር መሣሪያና በወታደራዊ ኃይል ይበልጥ ደርጅታ ኢትዮጵያን በተለያዩ አቅጣጫዎች ወረረች። ከአድዋው ዘመቻ ያልተሻለ የጦር ትጥቅ የነበራት ኢትዮጵያም የጣሊያንን ጦር በፅናት ተዋጋች። የወቅቱ ኃያላን እንግሊዝና ፈረንሳይ የጦር መሣሪያ በግዢ እንዳታገኝ ለጣሊያን ተደርበው ስላሴሩባት ኢትዮጵያ ብቻዋን ጦርነቱን በመጋፈጧ ድል ማግኘት አልቻለችም ነበር። የየግንባሮቹ የኢትዮጵያ የጦር አዛዦች ብዙዎቹ ሞተው ሠራዊቱም በመርዝ ጋዝና በአውሮፕላን ቦምብ ተደብድቦ ያለቀው አልቆ የቀረው ቀርቶ ጣልያን ጊዜያዊ ድል አግኝታ ዋና ዋና ከተሞችን ብትቆጣጠርም ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በገጠሩ ክፍል እምቢ ለነፃነቴ ፣ እቢ ለአገሬ ብለው የሽምቅ ውጊያ ጀመሩ።
ንጉሰ ነገስቱም ስደት ሄደው በጊዜው ለነበረው የመንግሥታቱ ማህበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) አቤቱታ አቀረቡ። የሚሰማቸው ግን አላገኙም። አርበኞች ግን ከቀን ወደ ቀን ድል እየተቀናጁ የጣሊያን ወታደሮችን መፈናፈኛ ፤ መግቢያ መውጫ አሳጧቸው። ከጣሊያን ወታደሮች ይማርኳቸው በነበሩ መሣሪያዎች ራሳቸውን እያደራጁ አብዛኛውን የገጠር ክፍል ተቆጣጠሩት። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መቀስቀስ ደግሞ ይበልጥ ለኢትዮጵያ ትልቅ ቦታ ነበረው።
የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲቀሰቀስ ጣሊያን የናዚ ጀርመን አጋር ሆነች፡፡ ያን ጊዜ እንግሊዞች የጣሊያን ጠላት ሆነው ኢትዮጵያን መደገፍ ጀመሩ። ስለዚህም ወታደራዊ ድጋፍ ሰጥተው፤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ረዷቸው፡፡ በጄኔራል ካኒንግሂም የሚመራው የእንግሊዝ ጦር ከኬንያ ተነስቶ ከደቡብ አቅጣጫ ወደ መሀል ኢትዮጵያ ሲገሰግስ ፤ በጄሪራል ፕላት የሚመራው ጦር ከሱዳን ተነስቶ ወደ አሥመራ ፤ ከዚያም ከሰሜን አቅጣጫ ወደ መሐል ኢትዮጵያ ተንቀሳቀሰ፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሚመራውና የአርበኞች ጦር እና የእንግሊዝ አማካሪዎች የሚገኙበት ጌዲዮን ተብሎ የተሰየመው ጦር ከሱዳን ተነስቶ በኦሜድላ አልፎ በጐጃም በኩል ወደ መሐል አገር ገሠገሠ፡፡ በመካከለኛ ኢትዮጵያ አርበኞች በጣሊያን ወታደሮች ላይ ጥቃትቸውን አፋፋሙ፡፡ ጣሊያኖች ክፉኛ ተሸነፉ፡፡ በየቦታው ድል የመሆናቸው ዜና ናኘ፡፡ ዘመቻው ከተጀመረ ሁለት ወራት ሳይሞላው ፤ ጣሊያኖች አዲስ አበባን ለቀው ፈረጠጡ፡፡ መጋቢት 28 ቀን 1933 ዓ.ም የጄኔራል ካኒንግሃም ጦር አዲስ አበባን ተቆጣጠረ።
እንግሊዞች ኢትዮጵያውያን አርበኞች ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ስላልፈለጉ ቀዳማዊ ኃይል ሥላሴን በደብረ ማርቆስ ለአንድ ወር ያህል እንዲቆዩ አደረጓቸው። ይሁንና በአዲስ አበባ በአርበኞች ተፅዕኖና ቅሬታ የተነሳ አርበኞች ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ፈቀዱ። ንጉሰ ነገስቱም አዲስ አበባ በታላቁ ቤተ መንግሥት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ሰቀሉ፡፡ አጼ ኃይለሥላሴ አዲስ አበባ ገብተው የሚከተለውን ንግግር አድርገው ነበር፡፡
‹‹ይህ የምትሰሙት ድምጽ የኔ የንጉሳችሁ የቀዳማዊ ሃይለ ሥላሴ ነው። አባቶቻችን ደማቸውን አፍሰው አጥንታቸውን ከስክሰው በነፃነት ያቆዩልን አገራችንን ወደ ከፍተኛው የሥልጣኔ ደረጃ ለማራመድ የምንደክምበት ጊዜ ከጥንት ጀምሮ ስለሆነ ደመኛ ጠላታችን ኢጣሊያ ይህንን እይታ ወሰናችንን ጥሳ የግፍ ጦርነት እንዳደረገችብን ሁላችሁም የምታውቁት ነው። እኛም በተቻለን ከተከላከልን በኋላ ርዳታ ለመጠየቅ ወደ መንግስታት ማህበር ወደ ወዳጆቻችን መንግስታቶች መጣን። እዚህ ስንነጋገር በቆየንበት ጊዜ የኢትዮጵያ አርበኞች ሰይፋችሁን ሳትከቱ ፊታችሁን ሳትመልሱ ሰንደቅ አላማችሁን ሳታጥፉ ለባዕድ አንገዛም በማለት በመሳሪያ ብዛት ከሚበልጣችሁ ጨካኝ ጠላት ጋር የባሕርይ የሆነውን ዠግንነታችሁን መሣሪያ አድርጋችሁ በኢትዮጵያ አምላክ ብቻ ተማምናችሁ በዠግንነት ቀንና ሌሊት በዱር በገደል ስትጋደሉ ቆይታችሁ ይኸው አሁን እንደምታዩት የማያቋርጥ የአምስት ዓመት ትግላችሁ የድካማችሁንና የመሥዕዋታችሁን ፍሬ ለማየት እንድትበቁ አደረጋችሁ።» በማለት አክብሮትን ለአርበኞች ሰጥተው ነበር። ንጉሱ ቀጥለውም እንዲህ ብለዋል፡፡
‹‹የሀገሬ የኢትዮጵያ ህዝብ!
ዛሬ ኢትዮጵያ እጆቹዋን ወደ እግዚያብሔር ዘርግታ እልል እያለች ምስጋናዋን የምታቀርብበት ደስታወንም ለልጆቹዋ የምትገልጽበት ቀን ነው። የኢትዮጵያ ልጆች ከባድ የመከራ ቀንበርና ከዘለአለም ባርነት ነፃ የወጡበት ቀንና እኛም አምስት ዓመት ሙሉ ተለይተነው ከነበረው ከምንወደውና ከምንናፍቀው ሕዝባችን ጋር ለመቀላለቀል የበቃንበት ቀን ስለሆነ ይህ ቀን የተከበረና የተቀደሰ በያመቱም ታላቁ የኢትዮጵያ በዓል የሚውልበት ነው። በዚህም ቀን ለሚወዷት ለአገራቸው ነፃነት ለንጉሰ ነገስታቸውና ለሰንደቅ አላማቸው ክብር ካባቶቻቸው የተላለፈውን ጥብቅ አደራ አናስዎስድም በማለት መስዕዋት ሆነው ደማቸውን ያፈሰሱትን አጥንታቸውን የከሰከሱትን ዠግኖቻችንን እናስታውሳለን። ለዚህም ለዠግኖቻችን የኢትዮጵያ ታሪክ ምስክር ይሆናል።
የጣሊያን መንግስት ኢትዮጵያን ድል አድርጎ ለመያዝ ችሎት ከሰጠው መሳሪያ በቀር ኢትዮጵያን ለመግዛት ሌላ ተስፋ ያደረገው ነገር ነበር። ይኸውም የኢትዮጵያ የነገድ ልዩነት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ እርሱ አሳብ አንደኛው ወገን ከሴም ዘር የመጣው የትግሬና የሸዋ፣ የጎጃም፣ የበጌምድር፣ በጠቅላላው አማራ የሚባለው፣ ሁለተኛው በኢትዮጵያ ምዕራብና ደቡብ የሚገኙትን እነወለጋ፣ እነጅማ፣ እነሲዳማ፣ እናሩሲ እነዚህን የመሳሰሉት አገሮች ከካም ዘር የመጡ በነገድም በቋንቋም በሃይማኖትም የተለያዩ ናቸው።
አንደኛው ወገን ቢያምጥብኝ ሁለተኛውን ወገን ይዤ አጠፋዋለሁ የማለት ተስፋ ነበረውና ይህንንም ሊሰራበት እንደጣረ በጉልህ ታይቷል። ዳሩ ግን የሶስት ሺህ ዓመት ባለው የነፃነቱ ዘመን በታሪኩ ውስጥ ምንም የሚያሳፍር ገጽ የሌለበት የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነቱን አሳይቶ ለጠላቱ ሳይመች ቀረ።››
ይሄ የኢትዮጵያውያን የድል ብስራት የሆነው የአርበኞች ቀን ከፍተኛ ዋጋ የተከፈለበት ነው። በዚህ ጦርነት ውስጥ ምላጭ ስቦ ጥይት ከተኮሰው አርበኛ በተጨማሪ በየቤቱ ሆኖ የተባበረውም ቀላል አልነበረም። በትግሉ ጊዜ የአርበኞች ዋናው ችግር ቀለብ ነበር። ቀለባቸውን የሚያገኙትም ከአርሶ አደሩ ቤት ነው። ይሄ ነገር የሚሆነው ታዲያ በግድም በውድም ነበር። ፈቃደኛ የማይሆን አርሶ አደር ካለ ፋና እስከማሰማራትም ተደርሶ ነበር። በተለይም ከጠላት ጋር የሚያብሩ ሰዎችን ደግሞ እህላቸው እንዲዘረፍና ለሰራዊቱ ቀለብ እንዲሆን ተደርጓል።
ሰራዊቱ ‹‹ደረቅ ጦር›› እና ‹‹መደዴ ጦር›› ተብሎ ለሁለት ተከፍለውም ነበር። ደረቅ ጦር የተባለው ሙሉ በሙሉ ውጊያ ላይ የሚያተኩር ሲሆን፤ ‹‹መደዴ ጦር›› የተባለው ደግሞ እንደሁኔታው የእርሻ ሥራ ላይ እንዲሰማራ ይደረጋል። ነገሩ ሲከፋ ግን አርበኞች ፍራፍሬ፣ ቅጠላቅጠልና የዱር አውሬ ሁሉ እየበሉ ተዋግተዋል። እናቶች ከሰራዊቱ ጋር አብሮ በመዝመት ምግብና ውሃ ከማቀበል በተጨማሪ ባህላዊ ህክምና እየሰጡ ሰራዊቱን ታድገዋል። የወደቀውን በማንሳት የቆሰለውን በመጠገን ተሳትፈዋል። ይህ የአርበኞች ቀን የሁሉም ኢትዮጵያዊ የተጋድሎ ድል ነው ማለት ይቻላል። በዚህ የአርበኞች የድል በዓል ላይ የሲልቪያ ፓንክረስት አስተዋፅዖም ሊጠቀስ ይገባል።
ሲልቪያ ፓንክረስት እንግሊዛዊት ናት። የኢትዮጵያ በፋሽስቶች መወረር ያንገበገባት ሴት ናት። ከኢትዮጵያ ንጉሥ ጎን በመቆም የኢትዮጵያ አርበኛ ሆነች። New Times and Ethiopian News የተሰኘ ጋዜጣ ማሳተም ጀመረች። ጋዜጣው በየሳምንቱ ለእንግሊዝ ፓርላማ አባላት የሚበተን ነው። ቀሪው ደግሞ ለሌሎች ታላላቅ ሰዎች የሚሰጥ ነው። ጋዜጣው ኢትዮጵያ ውስጥ ፋሽስቶች እየፈፀሙ ስላሉት አሰቃቂ ግፍ የሚገልጽ ነው። እንደ እንግሊዝ ያሉ ታላላቅ መንግሥታት ይህን ግፍ እንዲቃወሙ የሚቀሰቅስ ነው። በመጨረሻም የእንግሊዝ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጎን ቆሞ ፋሽስቶችን እንዲፋለም አደረገች። ሲልቪያ ፓንክረስት ኢትዮጵያን ታደገች ማለት ነው፡፡
የአርበኞች ቀን ጣሊያንን የማሸነፍ ድል ብቻ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ማን እንደሆነች ዓለም ያወቀበት የታሪክ ክስተት ነው፡፡ በዓድዋው ታሪክ የተደመመ የዓለም ህዝብ የጣሊያን ዳግም ወረራም ከሽፎ ማየቱ የበለጠ አስገራሚ ያደርገዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የአባት አርበኞች ገድል ለልጆች የአሸናፊነት ተምሳሌት ነው፡፡ ይህን የአባቶቹን ድል የሚያነብና የሚሰማ ትውልድ መሸነፍን አይቀበልም፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር እንበል፡፡ አንድ በተደጋጋሚ የምንሰማው ወቀሳ አለ፡፡ ይሄውም ወጣቱ ታሪኩን አያውቅም የሚል ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ ከወጣቱ የሚሰማው ወቀሳ መገናኛ ብዙኃንም ሆኑ ሌሎች አካላት ታሪክን ማሳወቅ ላይ ድክመት እንዳለባቸው ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህን ወቀሳ የሚያጠፉ ነገሮች እየታዩ ነው፤ ይሄውም ወጣቶች ለታሪክ ያላቸውን ትልቅ ትኩረት በተለያየ መድረክና በመገናኛ ብዙኃን እያየን እየሰማን ነው፡፡ መገናኛ ብዙኃንም ቢሆን ለእንዲህ አይነት ታሪካዊ ቀኖች በቀጥታ ሥርጭት ጨምሮ ሰፊ ሽፋን እየሰጡ ነው፡፡ ይሄ ነገር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ከወጣቱ በኩልም ወቀሳ ብቻ ሳይሆን ትኩረት መስጠትም ያስፈልጋል፡፡ በመገናኛ ብዙኃን የሚሰጠው ሽፋን ቀላል አይደለም፤ ከዚህ በላይ ደግሞ ያሉት የታሪክ መጻሕፍትም ቀላል አይደሉም፡፡ ክብር አገሪቱን በነጻነት ላቆዩን ጀግኖች አባቶቻችን!

ዋለልኝ አየለ

 

የታሪክ ማህደሩ - የድል ሐውልት

 

ጣሊያን ውስጡ ቂም ቋጥሮ ነበር። ከ40 ዓመት በፊት የሃፍረት ማቅ የተከናነበበት አድዋ ድል ለመበቀል ጥሩ ጊዜ ያገኘ መስሎታል። ከወልወል ግጭት በኋላ መስከረም 22 ቀን 1928 ዓ.ም የጣሊያን ጦር የመረብ ወንዝን ተሻግሮ በሦስት መስመር በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ከፍተ። በሰሜኑ ግንባር የመጨረሻ ጦርነት የሆነው የማይጨው ጦርነት መጋቢት 24 ቀን1928 ዓ.ም በሽንፈት ከተደመደመ በኋላ የፋሽስቱ ጦር ጉዞውን ወደ መዲናዋ አደረገ። ንጉሠ ነገሥቱ ሚያዝያ 24 ቀን1928 ዓ.ም አገር ጥለው ሲሰደዱ ጣሊያን ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ገባ። ሆኖም ጣሊያን ነገሩ አልጋ በአልጋ አልሆነለትም።
ከበጌምድርና አካባቢው ራስ ውብነህ ተሰማና ቢትውደድ አዳነ፤ ከጎጃም ቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬ፣ በላይ ዘለቀና ራስ ኃይሉ በለው፤ ከሸዋ ራስ አበበ አረጋይ፣ መስፍን ስለሺ ፀሐይ ዕንቁሥላሴ፤ የበሼ ቤተሰቦች ደጃች ተሾመና አበበ ሽንቁጥ፤ ከትግራይ ፊታውራሪ መስፍን ረዳ፤ ከደቡብና ምዕራብ እነራስ ደስታ ደምጠው፣ ገረሱ ዱኪ፣ መኮንን ደምሰው፤ ከወሎ እነ ኃይሉ ከበደ፣ ወሰን ኃይሉ፣ ከሐረርጌ እነ ደጃች ዑመር ሰመተር …. ወዘተ ለቁጥር የሚያዳግቱ ጀግና አርበኞችን እያስተባበሩ ፋሺስቱን ጦር መግቢያ መውጪያ አሳጡት።
በተለይ በነሞገስ አስገዶም እና አብረሃም ደቦጭ አማካኝነት የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በማርሻል ግራዚኒያ ላይ የቦምብ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ፋሽስቱ ጭፍጨፋ በማካሄዱ ለጣሊያን ብዙም የማይቃወሙ ሰዎች ጭምር ወደትግሉ እንዲገቡ በር መክፈቱን የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም መረጃ ቡድን መሪው አቶ ሳሙኤል ሠይፉ ይናገራሉ።
በአምስት ዓመቱ የአርበኝነት ተጋድሎ ወቅት የ«ጥቁር አንበሳ» አርበኞች ኅብረት የበረታ ትግል አድርገው የጥቁሮቿን አገር ነፃ አደረጓት። የኢትዮጵያ አርበኞች ለአገር ነፃነት ያበረከቱት በደም የተከፈለ አስተዋጽኦ ከዓለም አጥናፍ እስከ አጥናፍ ሲናኝ ይኖራል። የኢትዮጵያ ነፃነት የታወጀው መጋቢት 28 ቀን 1933 ዓ.ም ላይ ነው። ነገር ግን አፄ ኃይለሥላሴ በሱዳን በኩል ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ጣሊያን ከአምስት ዓመት በፊት አገሪቷን የተቆጣጠረበትን ቀን ለማስታወስ በሚመስል መልኩ ሚያዝያ 27 ቀን አዲስ አበባ እንዲገቡ ተደርጓል። ይህም ሆን ተብሎ እና ታቅዶ የተከናወነ ነው። ምክንያቱም ንጉሡ አዲስ አበባ ሲገቡ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ ነበር። አሁን በድል ሐውልት ጫፍ ላይ የሚታየው ሰዓትም ሰባት ሰዓት ላይ መቆሙ የዚሁ ታሪክ ማሳያ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ሐውልቱ ከነፃነት በኋላ ጥቅምት 23 ቀን 1936 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ተመርቆ ለእይታ ክፍት እንደሆነ የሚገልጹት አቶ ሳሙኤል፤ የሐውልቱ በር በስድስት ማዕዘን የተዋቀረ ሲሆን፤ ከበሀ ድንጋይ የተፈለፈሉ የሰው ምስል የያዙ ቅርጾች በዙሪያው ይዟል። የሐውልቱ ቁመት 15 ሜትር እንደሚረዝም ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የተገኘ መረጃ ያመለክታል። ከሐውልቱ ጫፍ ላይ የንጉሡ የዘውድ አገዛዝ ምልክት የሆነው የይሁዳ አምበሳ ተቀርጾ መቆሙን ይናገራሉ።
በሐውልቱ ላይ ተቀርጸው ከተቀመጡ ጽሑፎች መካከል ዝርዝር ጉዳይ የያዘው እና የአፄ ኃይለሥላሴን ንግግር ቃል በቃል ያስቀመጠው በሐውልቱ ዙሪያ እንደመቀነት ሆኖ በእብነበረድ ላይ የተቀረጸ ነው። ጽሑፉ በስተምዕራብ በኩል ወይም ፊቱን ወደ መዲናዋ እምብርት ፒያሳ የሚወስደውን መንገድ አድርጎ ባማረ የአጻጻፍ ስልት ተውቦ ይታያል። ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ንጉሠ ነገሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም በዋና ከተማቸው አዲስ አበባ ገብተው በቤተመንግሥታቸው የተናገሩት ዲስኩር ይላል። የንጉሡ ግርማ ሞገስ እና ነፃነት በመገኘቱ የነበረውን የህዝቡን ደስታ አስቡት። ፋሽስት ተባሮ የአገሬው ሰው መሪውን ፊት ለፊቱ ሲያይ የደስታ ሲቃ ሊተናነቀው እንደሚችል መገመት አያስቸግርም። በሐውልቱ ተቀርጾ የቀረው የንጉሡ ንግግርም ይህን ይመስላል።
«ያገሬ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም የታመናችሁ አርበኞች።» ይላል በትልቁ እንደ ርዕስ በሚመስል መልኩ። ከዚያም «የሰማይ መላዕክት የምድር ሠራዊት ሊያስቡትና ሊያውቁት ይቻላቸው ባልነበረ በዚህ በዛሬ ቀን ቸር እግዚያብሄር በመካከላችሁ ለመገኘት ስላበቃኝ በሰው አፍ የሚነገር ምስጋና የሚበቃ አይደለም። ከማናቸውም አስቀድሞ ለሁላችሁ ልነገራችሁና ልትረዱት የምፈለገው ይህ ቀን ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የአዲስ ታሪክ ዘመን መክፈቻ መሆኑን ነው። በዚህም በአዲስ ዘመን ሁላችንም መፈፀም ያለብን አዲስ ሥራ ይጀመራል።» ካለ በኋላ ጽሁፉ የተቀረጸበትን እብነበረድ ለመለየት በቀጭኑ በቁመት የወረደ ምልክት በማስቀመጥ ሌላውን ንግግር በቀጣዩ ክፍል ያስነብባል። ይኸውም እንዲህ የሚል ነው።
«በኢትዮጵያ ላይ ባለፉት ዘመናት የደረሰባትን መከራ ለማስታወስ ስንፈልግ ከዚህ ጋር የተያያዘውን ታሪኳን ብቻ ባጭር እንናገራለን። ከብዙ ሺህ ዓመት የበለጠ ነፃነቷን ጠብቃ የምትኖር ኢትዮጵያ ኢጣልያ ከጥንት ጀምሮ በነበራት አጥቂነት የኢትዮጵያን ነፃነት ለማጥፋት ስለተነሳች በ፲፰፻፹፰ ዓ.ም/1888 ዓ.ም/ በዓደዋ ላይ ጀግኖቿ ጦርነት አድርገው ነፃነቷን አዳነች። በዓደዋ ላይ ለተደረገው ጦርነት ምክንያት የሆነው የውጫሌ ውል ብቻ አይደለም። ነገር ግን ከዚያ በፊት ኢትዮጵያን ለመግዛት ኢጣሊያ የነበራትን ያላቋረጠ ምኞት ሲጠብቅ የነበረውን ምክንያት ያገኘ መስሎት ነበር። ኢጣልያ በዓደዋ ድል ከሆነች በኋላ እውነት ለምን ድል አደረገኝ ለማለት በኢትዮጵያ ላይ በአፍ ወዳጅ መስላ ስታዘጋጀው የነበርውን ምንም የአውሮፓ ያለፈው ታላቁ ጦርነት ቢያቋርጣት በአለፉት ዘመናት ገለጠች።» በማለት ደግሞ አሁንም መክፈያውን በመጠቀም ዙሪያውን እየተሽከረከረ ሌላ ንግግራቸውን ያመላክተናል። ኃይለሥላሴ አሁንም ንግግራቸው አይቋረጥም። እንዲህ ሲሉ ከህዝቡ ጋር ያወራሉ።
«ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ የአጥቂነት ጦርነት ባደረገች ጊዜ ምንም እንኳን በጦር መሳሪያ ተወዳዳሪ አለመሆናችንን ብናውቀው በግፍ አገራችንን ለመንጠቅ የመጣብንን ጠላት መከላከል የተገባን ሥራ ስለሆነ በነበረን አቅም ተከላከልን። የዓለም ህግ በከለከልውም መሳርያ በጋዝ ጭስ ሕዝባችንን የምትጨርስብን ቢሆን ወደ ዓለም መንግሥታት ለማሰማትና ፍርድ ለመቀበል ሄድን። ነገር ግን ይህ ኢጣልያ ያነሳችው ጠብ በዓለም ላይ ሁሉ የሚዘረጋ ስለሆነ ዓለምም አሁን ከደረሰባት ጥፋት ለማዳን ለመንግሥት መሪነት አላፊነት የተቀበሉ ሁሉ የሚጣጣሩበት ዘመን ስለነበረ ይህ እሳት እንዳይቃጠል በዓለም ስምምነት እንዲገኝ ሲደክሙበት ቆዩ።
በዚያም ዘመን የልብ ወዳጃችን የሆነችው ታላቂቱ ብሪታኒያ በመልካም ወዳጅነት ተቀብላን ቆየች። በዚያም ያለፍርድና ያለርህራሄ በከንቱ ደማቸው በኢጣልያ እጅ የሚፈሰውን ያገሬን ሰዎችና በከንቱ የሚቃጠሉትን አድባራት እና ቤተክርስቲያናት፣ በሰው አገር ተሰደው፣ በአገራቸውም ላይ በዱር በገደልና በጫካ መከራና ሥቃይ ያዩ የነበሩትን በአሳብ ሳንለያቸው በሥራ ቆየን። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ኢጣልያ በጭካኔ የፈጀቻቸው ወጣቶችና ሴቶች፣ ካህናትና መነኮሳት ስንት ናቸው?
በ፲፱፻፳፱ ዓ. ም /በ1929 ዓ.ም/ የካቲት ሚካኤል ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በሦስት ቀን ውስጥ ማለቃ ቸውን ታውቃላችሁ። በአካ ፋና በዶማ፤ በምሳርና በመ ዶሻ የተፈለጡት፤ በሳንጃ የተወጉት፤ በዱላና በድንጋይ የተወገሩት፤ በቤታቸው ውስጥ እንዳሉ ከሕፃናት ልጆቻቸው ጋር በእሳት የተቃጠሉት፤ ታሥረውም በረሃብና በውሃ ጥም ያለቁት ደማቸውና አጥንታቸው አቤቱታውን ሲያቀርብ ቆየ። ይህ እንደዚህ ያለው የአረመኔና የጨካኝነት ሥራ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሳይሆን የባሰውን በቀሩት በሌሎች የኢትዮጵያ አገሮች ውስጥ ሲሠራ እንደነበረ ማንም የሚያውቀው ነው። ተይዞ ያልተደበደበ፣ ያልተረገጠና ያልተዋረደ ያልታሠረ አይገኝም።» ይህ ደግሞ በጣም ረጅምና መቆረጥ የማይችልን ጽሑፍ የያዘ ነው። ያው ከላይ እንደተባለው መለያውን እየተጠቀመ ጎላ ጎላ ብሎ ፊዳላቱን ከነ ሁለት ነጥቦቹ ያስቀምጣቸዋል። ግን ሃሳቡ አሁንም አልተቋጨም። እንዲህ ሲል ይቀጥለዋል።
«አሁን በፊታችን ወዳለው ወደአዲሱ ታሪክ እንተላለፋለን። የዛሬ አምስት ዓመት ልክ በዛሬዪቱ ቀን የፋሺስት ወታደር ከዋናው ከተማችን ገባ። ቀጥሎም ሙሶሊኒ በኛ አገር በኢትዮጵያ ውስጥ የሮማን አምፒር አቁሜያለሁ ብሎ ለዓለም አስታወቀ። አቀናሁላችሁ ብሎ ያስታወቀውም አገር ለዘላለም በጁ የሚኖር መስሎት አምኖ ነበር። የኢትዮጵያ ህዝብ ጀግንነት በታሪክ የታወቀ ነው። ነገር ግን ለህዝባችን የሚያስፈልገውን የዘመኑን መሳሪያ የምናገባበት ጠረፍ ባለመኖሩ ምክንያት ለማግኘት ሳይቻለን ቀረ። ሙሶሊኒ በሠራው ሥራ ፶፪ /52/ መንግሥታት ፈረዱበት። እርሱ ግን ይህን የግፍ ሥራውን ተመካበት እንጂ ፍርዳቸውን ከምንም አልቆጠረውም። ያለፉት አምስት ዓመታት ለናንተ ለሕዝቦቼ የጨለማ ጊዜያቶች ነበሩ። እናንተ ግን ተስፋ ሳትቆርጡ ትቂት በጥቂት እየጀመራችሁ በኢትዮጵያ ኮረብቶች ላይ ተሰማራቹ። በእነዚህ በአምስት ዓመታት ውስጥ እናንት የኢትዮጵያ አርበኞች ማናቸውንም መከራና ጭንቀት ችላችሁ ነፃነታችሁን ጠብቃችሁ ወደ ተሰማራችሁባቸው ተራሮች ለመምጣት ጠላታችን ከቶ ሊደፍር አልቻለም።
ምንም እንኳን አገሩን ለማቅናት ባይችል የያዘውን አሠለጥናለሁ በማለት ብዙ ሺህ ሚሊዮን ሊሬ አፈሰሰ። ይህን ሁሉ ገንዘብ ማውጣቱ የተጠቃውን የኢትዮጵያን ህዝብ ሁኔታ ከፍ ለማድረግ ወይም የሠራውን ግፍ ለማሻሻል አልነበረም። ነገር ግን በቅድስት አገራችን በኢትዮጵያ የፋሺስት ኮሎኒ ለማቆምና እሱ እንዳሰበው ያለ የጭካኔ አገዛዝ ለመትከል ነበር። የኢትዮጵያን ዘር ለመጨረስ ተጣጣረ እንጂ ምንም ላንድ ነፃ መንግሥት ከባድ ቀንበር ሆኖ የሚቆጠር ቢሆን የማንዳ ወይም የፕሮቴክትራ አስተዳደር እንኳ አላሰበላትም። ነገር ግን ይህ በብዙ ሺህ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብና የተዘጋጀው የጦር መሳርያ ሁሉ ሙሶሊኒ ላሰበው መንገድ ማዋሉ ቀርቶ በፍፁም ላላሰበው ጉዳይ ሆነ።
ኢጣልያ ድል ከሆነችው ከፈረንሳይ ላይ የተቻላትን ያህል ለመናጠቅ አስባ ጦርነት ለማድረግ መቁረጧን በገለጠች ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ያጋዘችው ሰው፤ የላከችው ገንዘብና መሳርያ ከልክ ያለፈ ነበር። የሰበሰበችው ደምበኛ ጦር ቁጥሩ ከ፻፶ ሺህ /150 ሺ /አያንስም፤ የተከበብሁም እንደሆን ብላ የብዙ ዓመት ስንቅ አከማችታ ነበር። በዚሁ ባዘጋጀችው የጦር መሳሪያ በመተማመን ሊያሸንፈኝ አይችልም ብላ ስለተመካች የፋሺስት መንግሥት የቶታሊታሪያን አገዛዝ ባገራችን ውስጥ ለመትከል ጀምሮ ነበር። ነገር ግን የፋሺስት መንግሥት ያላሰበው ነገር መጣ።
ለዛሬው ዘመን ጦርነት ዋና አስፈላጊ የሆነው የተዋጊነት መንፈስ በናንተ ተገለጠ። ጀግንነትና ርህራሄ ያለው የአንድ አገር ህዝብ ከመሆናችሁ ጋራ እርስ በርሳችሁ በመረዳዳታችሁ የጦር እቅድ በማወቃችሁ፤ በመሣሪያና በጦር ሰራዊት ከናንተ እጅግ ከፍ ያለውን ጠላት ለማጥፋት በቃችሁ። ለሰው ልጅ የነፃነት መብት ሲሉ በሌላ ክፍል ይዋጉ የነበሩት የኢንግሊዝ ወታደሮች ኢትዮጵያን ለመርዳትና ነፃ ለማውጣት እስኪዘጋጁና እስኪታጠቁ ድረስ፤ ጊዜ አስፈልጓቸው ነበር። የኢትዮጵያ አርበኞች ግን በመላው ኢትዮጵያ መገናኛ መንገዱን እየቆረጣችሁ ጠላታችንን እያስጨነቃችሁ ከየምሽጉ እንዳይወጣ አደረጋችሁት። ምንም እንኳ የተማመኑበት ወታደር ቁጥሩ እጅግ ብዙ ቢሆንም የኢትዮጵያ ሕዝብ እሱንና አገዛዙን ከዳር እስከ ዳር እንደጠላው በቶሎ ተረድቶ ይህን በመሰለ አገርና ህዝብ መካከል መኖር የማይቻለው መሆኑ ታወቀው። እንደልማዱም የመርዝ ጋዝ ቦምቡን እየጣለ የአረመኔነትና የጭካኔ ሥራውን እየሠራ ውስጡ በመነመነ በላይነት እኖራለሁ ብሎ ለማሰብ የማይቻል ሆነበት።» ብሎ ለዓይናችን እርፍታን ይሰጠናል። በአራት ማዕዘን ቅርጽ ውስጥ በሲቢንቶ የተሠራ ኮኮብ ያሳየናልና አሁንም በሐውልቱ እየዞርን እንድናነብ የሐሳቡ ፈሰት ይገፋናል።


በሌላኛው የሐውልቱ ጎን ጽሑፉ ሲቀጥል «በያለበት ከቦ የያዘው ወታደር ከእርሱ የበለጠ ኃይለኛ ባላጋራ መሆኑን ተረዳው።» ብለው ንጉሡ ንግግራቸውን መቀጠላቸውን ያስረዳናል። «ይህንንም ባላጋራውን ለመግጠም ያቺኑ ተርፋ የነበረችውን ድፍረት እና ገንዘቡን ሁሉ አጠፋ። ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ የምጠጋበት ደኅና ቦታ አገኝ እንደሆነ በማለት ሞከረ፤ ነገር ግን አንድም የሚጠጋበት ቦት አላገኘም። ጊዜው ሲደርስ የቃልኪዳን ረዳታችን የታላቁ የእንግሊዝ መንግሥት ጠላታችንን በሚገባ ለመውጋት ተደራጀ። እኔም ይህን እንዳወቅሁ ወታደሮቼን ይዤ በምዕራብ በኩል ከሚዋሰነን እሩቅ ከሆነው አገር ከሱዳን ተነስቼ ወደ መሀል ጎጃም ገባሁ።
ጠላታችን በጎጃም መሬት ብርቱ ምሽጎችና ኃይለኞች ወታደሮች፤ ኤሮፕላኖችና መድፎችም ነበሩት። የኛንና የጠላታችንን ወታደሮች ቁጥር ስንገምተው የብልጫው ከፍተኛነት የኛ አንድ፤ የእርሱ ፳ /20/ ይሆን ነበር። ከዚህ በቀር ደግሞ እንደፈቃዳችን የምናዝዝበት መድፍና ኤሮፕላን አልነበረንም። የኔ በአርበኞቼ መካከል መገኘት ብቻ ብዙ ሺህ ሰው ባንድ ጊዜ ሳበ። የጠላታችንም ፍርሐቱና መጨነቁ በዚያው መጠን እየበዛ ሄደ። ወታደሮቼ እየገሰገሱ የጠላታችንን መገናኛ መንገድ እየቆረጡ፤ ወታደሮቹንም እያባረሩ ከአባይ ወዲያ ማዶ አሻግረው ወደ ሸዋና ወደ ቤጌምድር ሲከታተሉ ሳሉ፤ የእንግሊዝ እምፔሪያል ወታደሮች ማንም ሊተካከለው በማይችል ሁኔታ እየገሰገሱ ዋና ከተማችንን መያዛቸውንና በስተ ሰሜን በኩል ወደ ደሴ፣ በስተ ደቡብ በኩል ወደ ጅማ የመግፋታቸውን ደስ የሚያሰኝ ወሬ ሰማሁ።
እንደዚሁም ከሱዳን የዘመቱት ወታደሮች እጅግ በሚያስደንቅ ኃይል የከረንን ምሽግ አፍርሰው የጠላትን ጦር በፍፁም ድል አደረጉት። እኔም ወደ ዋናው ከተማዬ የምገባበት ጊዜ ስለደረሰ ጠላታችንን ለማባረር በየቦታው ተበታትነው የነበሩትን ወታደሮቼን ሰብስቤ ዛሬ በዋናው ከተማዬ ተገኘሁ። ወታደሮቼን እየመራሁ በመንገዴ ላይ የነበረው ጠላት ድል እየሆነ እስከዚህ በመድረሴና የጋራ ጠላታችንን ኃይል በመስበሬ ደስታዬ ሳያቋርጥ ይመነጫል። የፋሺስት መንግሥት ጥሎት በሸሸው ቤተመንግሥቴ ውስጥ ዛሬ በመካከላች በመገኘቴ ሁሉን ቻይ ለሆነው አምላክ የማቀርብለት የልብ ምስጋና ሊወሰን አይችልም።» በማለት ሌላ ርዕስ ይሰጠናል። ይኸውም « ያገሬ፡ የኢትዮጵያ፡ ህዝብ።» በሚል በትልቁ ተጽፎ ሀተታውን ይቀጥላል።
«ዛሬ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ዘርግታ እልል እያለች ምስጋናዋን የምታቀርብበት፤ ደስታዋን ለልጆቿ የምትገልጽበት ቀን ነው። የኢትዮጵያ ልጆች ከባዕድ የመክራ ቀምበርና ከዘለዓለም ባርነት ነፃ የወጡበት ቀንና እኛም አምስት ዓመት ሙሉ ተለይተንው ከነበረው ከምንወደውና ከምንናፍቀው ህዝባችን ጋራ ለመቀላቀል የበቃንበት ቀን ስለሆነ ይህ ቀን የተከበረና የተቀደሰ በየዓመቱም ታላቁ የኢትዮጵያ በዓል የሚውልበት ነው። በዚህም ቀን ለሚወዷት ለአገራቸው ነፃነት፤ ለንጉሠ ነገሥታቸውና ለሰንደቅዓላማቸው ክብር ከአባቶቻቸው የተላለፈውን ጥብቅ አደራ አናስወስድም በማለት መስዋዕት ሆነው ደማቸውን ያፈሰሱትን፤ አጥንታቸውን የከሰከሱትን ጀግኖቻችንን እናስታውሳለን። ለእነዚህም ለጀግኖቻችን የኢትዮጵያ ታሪክ ምስክር ይሆናል።
በአለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በዝርዝር ተነግረውና ተቆጥረው የማያልቁ ያገኘናቸው መከራና ስቃይ ትምህርት ሆነውን ሠራተኛነት፤ አንድነት፤ ኅብረትና ፍቅር በልባችሁ ተጽፈው ለምናስበው ለኢትዮጵያ ጉዳይ ረዳቶች ለመሆን ዋና ትምህርት የሚሰጣችሁ ነው። በአዲሷ ኢትዮጵያ ከእንግዲህ ወዲያ የማትነጣጠሉ፤ በህግ ፊት ትክክለኛነትና ነፃነት ያላችሁ ህዝቦች እንድትሆኑ እንፈልጋለን። አገር የሚለማበትን፤ ህዝብ የሚበለጽግበትን እርሻ፤ ንግድ፤ ትምሕርትና ጥበብ የሚሰፋበትን፤ የሕዝባችን ህይወቱና ሀብቱ የሚጠበቅበትን፤ ያገር አስተዳደርም በአዲሱ ሥልጣኔ ተለውጦ ፍጹም የሚሆንበትን ይህን ለመሰለው ለምንደክምበት ሥራ አብሮ ደካሚ መሆን አለባችሁ።
ይህንን እግዚአብሄር በቸርነቱ የሠራልንን ሥራ፤ መጀመርያ የቃል ኪዳን ረዳታችን የእንግሊዝ መንግሥት ያደረገልንን ውለታ ለመመለስ ኤምፔሪያል ትሩፕ የተባሉት ወታደሮች ወደ ሌላ የጦር ግንባር ተዛውረው የጋራ ጠላታችንን ለማጥቃት እንዲችሉ ማድረግና በጦር ሠራዊትም እንድናግዝ የሚያስፈልግ ሆኖ ሲገኝ በመርዳት፤ ሁለተኛም በአገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ ሃይማኖትን የሚያስከብርና የሚጠብቅ መንግሥት በማቋቋም የሕዝብንና የህሊናን ነፃነት በመፍቀድ ለሕዝብና ላገር የሚጠቅም ሥራ ለመሥራት ብርቱ ምኞታችንና ሃሳባችን ነው።
አሁም በመጨረሻው ለናንት ለሕዝቤ የማስታውቃችሁ ዛሬ የሁላችን የደስታ ቀን መሆኑን ነው። ዛሬ ጠላታችንን ድል የመታንበት ቀን ነው። ስለዚህ በሙሉ ልባችን ሁላችን ደስ ይበለን ስንል ደስታችን በክርስቶስ መንፈስ እንጂ በሌላ አይሁን። ለክፉ ክፉ አትመልሱ፤ ጠላት እንደወትሮው ልማድ እስከዚህ መጨረሻ ሰዓት ድረስ እንደሠራው ያለ የጭካኔና የግፍ ሥራ አትሥሩ። ጠላታችን መውቀሻ በሚሆነው ነገር የኢትዮጵያን መልካም ስም እንዳታሳድፉ ተጠንቀቁ። ጠላቶቻችን በእጃቸው ያለውን መሣሪያ እንዲያስረክቡና በመጡበት መንገድ ተመልሰው እንዲሄዱ እናደርጋለን።
ደራጎንን የገደለ ቅዱስ ጊዮርጊስ የኛም የባለቃል ኪዳን ረዳቶቻችንም የጦር ሠራዊት ባልደረባ ነውና ይህን አዲስ የተነሳውን የሰውን ልጆች የሚያስጨንቀውን እግዚአብሄርን የማያምን ጨካኝ ዘንዶ ለመቃወም እንድንችል ለዘላለም ፀንቶ በሚኖር ወዳጅነትና ዝምድና ከባለቃል ኪዳን ረዳቶቻችን ጋራ እንተሳሰር። እነርሱንም እንደ ዘመድና ወዳጅ ተመልክታችሁ ደግነትና ቸርነት እንድታሳዩዋቸው አደራ እላችኋለሁ።» ይላል ሙሉ ንግግሩ በሐውልቱ ላይ ተቀርጾ ለኢትዮጵያውያን የተላለፈው መልዕክት። ከታች ደግሞ በርከት ያሉ ሥዕሎች ከእነ መልዕክታቸውና ምስላቸው ጽሑፉን አቅፈው ይዘውታል። ያው ምሰሶ በመሆን እያገለገሉ ናቸው ብሎ መፈረጅ ይቻላል።
ጥቂቶቹን ለማንሳት ያህል «አምስት ዓመት ሙሉ በጠላት የጭቆና ቀንበር ውስጥ ተቀምጠው የሞት ጥላ በራሳቸው ላይ እያንዣበበ ሃሳባቸውን ከአርበኞችና ከስደተኞች ሳይለዩ አገራቸውን በስውር ላገለገሉ የውስጥ አርበኞች የቆመ መታሰቢያ» ይልና ከላዩ አንድ እንስት ጦርና ጋሻ ይዛ ይታያል። ሌላው ደግሞ ከጠላት ጋራ ተስማምቶ ከመኖር ሞቱን መርጦ በጦር ሜዳ ላይ የሚገኘውን ሠርቶና ደሙን አፍስሶ አምስት ዓመት ሙሉ ሲታገልና ሲሟገት በሰማያት ላይ ኖሮ እንደገና ከእግዚአብሄር ጋራ በድል አድራጊነት ጠላትን አባሮ ሰንደቅ ዓላማችንን ለመለሰልን ለቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የቆመ የዘላለም መታሰቢያ» በማለት የንጉሡን ፎቶ ከእነ አንበሳው ያሳየናል። በዙሪያው ሌሎች ምስሎችም አሉ። ግን ለዛሬ ይህ ይበቃልና ክብር እና ፍቅር አገራችንን ላቆዩ አባቶች! ይሁን።

ጌትነት ተስፋማርያም

 

ከባለውለታዎቻችን መካከል ጥቂቶቹን 

 

የዛሬ የ«ሕይወት እንዲህ ናት» አምዳችን ቀኑን የዋጀ ቅኝትን ይዟል። እንደሚታወቀው ትናንት ያከበርነው ባለውለታዎቻችንን ነው። እናም በዚህ አምድም ከብዙዎቹ ውስጥ ጥቂቶቹን በማንሳት ሕይወታቸውን በወፍ በረር ቅኝት ለማስዳሰስ ይሞከራል። ምክንያቱም እነርሱ ዘንድ ብዙ አለ፤ ግን ውለታቸው ምን ነበረ የሚለውን ብቻ ለማሳየት ጥቂት እንላችኋለን። ጣሊያን ዓድዋ ላይ የተከናነ በችውን ሽንፈት ለመበቀል ስላቃታት ለአርባ ዓመታት ያህል ስትዘጋጅ መቆየቷን ማንም የሚረዳው ነው። ስለዚህም ኢትዮጵያን በጦርነት ማሳፈር አትችልምና በየጊዜው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ እንዲ ሁም በባህል መስክ ግንኙነት ለማድረግ ትጥር ነበር።

እንዲያውም የተፈራረመቻቸው የሰላምና የትብብር ውሎች ነበሯት። ታዲያ አሁንም ይህንን ሁኔታዋን ወደ ኃይል ከማምጣቷ ጋር ተያይዞ ለሚያስገድዳት እጅ ሰጥታ የማታውቀውን አገር ማወዛገብ ቀጠለች። ግን ዛሬም ቢሆን አገሪቱ በጠመጃ አፈሙዝ አስገድዳ ድልን ወደራሷ አድርጋለች። ታዲያ ለዚህ መሠረቱ ማንም አልነበረም፤ ጀግኖቹና አይበገሬዎቹ ሕዝቦቿ ናቸው።
በአገሩና በነፃነቱ የማይደራደረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የፋሺስትን አገዛዝ “አሜን” ብሎ አልተቀበለውምና ማቄን ጨርቄን ሳይል ለነፃነቱ ተፋልሟል። ታዲያ ይህንን ፋሺስትን የማራቆት ዘመቻን በድል የተወጡት እልፍ የነፃነት ፋኖዎች በመሆናቸው ስለነእርሱ ቢወራ አያልቅም። የቱስ ተነስቶ የቱ ይቀራል። ሆኖም ልዘርዝር ቢባልም “ዓባይን በጭልፋ” ቢሆንብንም እንዳይረሱና ትውልዱ እንዲያው ቃቸው ለማድረግ ጥቂቶቹን ለማንሳት ወደናል። ታሪክ እንዳይደበቅ ትውስታ ያስፈል ጋልናም ከተለያዩ ምንጮች በአሰባሰብነው መረጃ እንካችሁ አልን። መልካም ንባብ።

ሸዋረገድ ገድሌ - የአኩሪ ገድላት ባለቤት


የወንዶች ስም በጀግንነት የታሪክ መዝገብ ላይ ብዙ ጊዜ በስፋት ተጽፎ ይገኛል። ይሁንና ሴቶች በማንኛውም የነፃነት ተጋድሎ ላይ ጉልህ ድርሻ ቢኖራቸውም ብዙ ሲነገርላቸው አይስተዋልም። ስለእነርሱ የተጻፉ ነገሮችም ጥቂቶች ናቸው። የአርበኛዋ ሸዋረገድ ገድሌም ዕጣ ፈንታ ይህ ነበር። ነገር ግን ታሪክ የማይሽረው ሥራ ሰርታለችና በወቅቱ ያሉትን ሰዎች አብነት በማድረግ ዛሬ ላይ ታሪካቸውን እንድናውቅ ሆኗል። እናም ታላቋ አርበኛ ክብርት ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ ብዙ አኩሪ ድሎችን ካደረጉት ሴት አርበኞች መካከል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡


አርበኛዋ ሸዋረገድ «የሀገር ፍቅር ማህበር» ሲቋቋም በማህበሩ ከተመዘገቡት መካከል የመጀመሪያዋ ሴት ናቸው። የቤተ-ክህነት ተማሪም ነበሩና «ትዳር አልፈልግም» በማለት ለምናኔ እየሩሳሌም መጓዛቸው ይነገራል። በአገራችን ታሪክ ከመጀመሪያዎቹ የባንክ ተጠቃሚዎችና የአክሲዮን ገዥዎች መካከልም እርሳቸው አንዷ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል። የሸዋረገድን ስም ይበልጥ እንዲደምቅ ያደረገው ታሪክ ግን የአርበኝነት ተጋድሎአቸው ሲሆን፤ የጣሊያ ጦር አገራችን እንደገባ የመጀመሪያ ተግባሩ ያደረገውን ለዘመናት በድል ሲውለበለብ የቆየውን የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ማውረድና የራሱን ባንዲራ ማውለብለቡን የተቃወሙ ናቸው።
በወቅቱ ለተቃውሞው መነሻ ያደረጉት «አገሬ ተወረረች፣ ተዋረደችም» ሲሉ አምርረውና ጮኸው ማልቀሳቸውን ነበር። ሁኔታቸውን ያዩ የጣሊያን ሹማምንቶችም የእርሳቸውን ድርጊት ድፍረት እንደሆነ አምነው ለክስ አቀረቧቸው። ለምን አለቀስሽ ሲሉም ጠየቋቸው። እርሳቸውም «አዎ አልቅሻለሁ፣ የአገሬን መወረርና መዋረድ ያወቅሁት የእኛ ሰንደቅ አላማ ወርዶ የእናንተ ሲወለበለብ በማየቴ ነው። ሰው ለእናት አገሩ ቢያለቅስ ነውሩ የቱ ላይ ነው?» በማለት እልህ በተሞላ ሁኔታ መልስ ሰጥተዋል። ይህ ሁኔታቸው ደግሞ አሳስሯቸው እንደነበር ታሪክ ያወሳል።


ወይዘሮ ሸዋረገድ ለአርበኞች ስንቅ በማቀበል፣ መሣሪያ በመግዛትና በማዘዋወር፣ መረጃዎችን በማሰባሰብ፣ መድኃኒቶችን በመላክና ለተዋጊ ወገኖቻቸው የሞራል ድጋፍ በማበርከት የተጋድሎ ዓመታት ያሳለፉ ናቸው። ይህ ድርጊታቸው ደግሞ ለጣሊያኖቹ ሰላም አልሰጠም። ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት በዘለለም ለክስ እንዲቀርቡ አድርጓቸውም ነበር። ሆኖም ስለፈፀሙት ድርጊት ኩራት እንደሚሰማቸውና ይህን ማድረጋቸው ለአገራቸው ክብር ሲሉ እንደሆነ በድፍረት መናገራቸውን አላቋረጡም። እንዲያውም በጦርነቱ ዋዜማ በ1927 ዓ.ም ለተቋቋመው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ንብረታቸውን ሸጠው በማስረከብ አገር ወዳድነታቸውን አስመስክረዋል።
ኢትዮጵያውያን ወይዛዝርት ከየቤታቸው እራፊ ጨርቆችን እንዲያሰባስቡ በማድረግም ለቁሰለኞች እንዲላክ ያደርጉ ነበር። ከዚህ ባሻገርም የጠላት መረጃዎችን በማሰባሰብና ወደ አርበኞች በምስጢር እንዲደርስ በማድረግ ታላቅ ተግባር ፈፅመዋል። በዚህ ሥራቸው ደግሞ ጥርስ የነከሱባቸው ጣሊያኖች ሕይወታቸውን በእስር እንዲገፉና ቆይቶም ሞት እንዲፈረድባቸው ወሰኑባቸው። ሆኖም አዚናራ ወደምትባልና ሰሜናዊ ምዕራብ ወደምትገኝ ደሴት ታስረው እንዲቆዩ ፍርዱ በመቀየሩ የእስር ዘመናቸውን በደሴቱ እንዲገፉ ቁርጥ ሆነ። እርሳቸው ግን የቦታ ለውጥና ርቀት አልበገራቸውም፤ ትግላቸውን አጠናከረላቸው እንጂ። በማረሚያ ቤቱም የሚቀርበውን ምግብ በአሳሪዎች ፊት በመድፋትና ጦማቸውን ውለው በማደር ተቃውሟቸውን ያሳዩ ነበር። በዚህ ሁኔታም ከአንድ ዓመት በላይ ታሰሩ፡፡ «ታርመዋል» በማለትም እንዲፈቱ ተወስኖ አዲስ አበባ ገቡ።


አዲስ ዓለም ይገኝ የነበረው የጣሊያን ምሽግ ኅዳር 5 ቀን 1933 ዓ.ም ሲሰበር ጠቃሚ መረጃዎችን ለአርበኞች በማሰባሰብና በርካታ እቅዶችን በመንደፍ ታላቁን ድርሻ የሸፈኑት ሸዋረገድ ገድሌ፤ ምሽጉ ከተሰበረም በኋላ ደጀን መሆኑን ትተው ወደ ውጊያ ለመግባት በመወሰናቸው ከሻለቃ በቀለ ወያና፣ ከደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ጦር ጋር ተሰልፈው ጠላትን ተፋልመዋል። በጦርነቱ የአራት ሰዓታት ውጊያ ላይ ጠላት በጣለው ድንገተኛ አደጋም ተማርከው ነበር። በጣሊያኖች እጅ ዳግመኛ በመውደቃቸው ደግሞ የፊጥኝ ታስረው ወደ እስር ተወርውረዋል። ይሁን እንጂ ጣሊያን ውርደትና ሽንፈት በ1933 ዓ.ም ሲከናነብ ታላቋ አርበኛ ሸዋረገድ ገድሌ ነፃ ወጡ።
ቀድሞ የጀመሩትን አርበኞችን የመርዳት ተግባር አጠናክረው የበጎ አድራጎት ሥራን የቀጠሉት ሸዋረገድ፤ በንግዱ ዘርፍ ተሰማርተው በርካቶችን ጠቅመዋል። ሆኖም ጥቅምት 22 ቀን 1942 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ይህን የሰማው ሕዝብም እንዲህ ብሎ አንጎራጉሮላቸው ነበር ይባላል።
እናንት ወጥ ቤቶች በርበሬ ቀንጥሱ፣
እናንት ስጋ ቤቶች ሰንጋውን ምረጡ፣
ሸዋረገድ ገድሌ ለገና ሲመጡ።
ቤተሰቧ ሰፊ ገናና ጥምቀት፣
ሸዋረገድ ገድሌ እንደምን ትሙት።

ራስ ደስታ ዳምጠው


በ1886 ዓ.ም ሰሜን ሸዋ ውስጥ ተወለዱ። አባታቸው ፊታውራሪ ዳምጠው ከተማ በአድዋ ጦርነት ትልቅ ጀግነት ሰርተው እንደተሰዉ ይነገራል። ታዲያ የአባታቸውን መርህ የተከተሉት ራስ ደስታም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ፖለቲካ ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገው ነበር ሰማዕትነትን የተቀበሉት። እንዲያውም ለአገር ክብር ካበረከቱት አስተዋጽኦ አንጻር ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ልጃቸውን ተናኝወርቅ ኃይለሥላሴን እንደዳሩላቸው ይወሳል።


ራስ ደስታ የውጭ ዓለማትን የመጎብኘት ዕድላቸው ሰፊ በመሆኑ የውጭውን ሥልጣኔ ወደ አገራቸው ለማምጣት ሰፊ እንቅስቃሴ አድርገዋል። ጣሊያን ወረራ ባደረገ ጊዜ ራስ ደስታ የሲዳማ አገረ ገዥ ነበሩ። ስለዚህም በነገሌ ቦረና በኩል የመጣውን ጠላት ለመመከት ዘምተዋል። በሱማሊያ በኩል የመጣውን ጠላትም ማጥቃታቸው ይገለፃል። ትልልቅ ውጊያዎችንም በማይጨው ላይ ከደጃዝማች በየነ መርዕድ ጋር ያካሄዱ ናቸው። ራስ ደስታ ዋና ዋና አሽከሮቻቸውን ፊታውራሪ አደመንና ፊታውራሪ ታደመን በመያዝ እስከ ጣሊያን ግዛት ዶሎ ጫፍ ድረስ በመጓዝ በጣሊያን ሱማሊያ ግዛት ውስጥ ታላቅ ፍርሃት ፈጥረው ነበር። ግራዚያኒም በሱማሊያ ያለው መቶ ሺህ ጦር የሚበቃኝ አይደለምና ሌላ ረዳት ላኩልኝ እያለ ወደ ሙሶሎኒና ወደ ባዶልዩ ቴሌግራም ሲልክ የነበረው የእነርሱ ኃይል ከባድ መሆኑን በመረዳት ነበር።
በሱማሊያ ግዛት ውስጥና በየመንደሩ ነዋሪ ሱማሌዎችን ባዋጅ እየሰበሰበ … «ይሄው ኢትዮጵያውያን ሱማሊያን ለመውረር ተሰልፈዋል። እኛም እንደሚገባ ተዋግተን ድል የሆንን እንደ ሆነ በመርከባችን ተሳፍረን ወደሀገራችን እናመልጣለን። እናንተ ግን የምትሄዱበት ስፍራ የላችሁምና በወረሯችሁ ጊዜ … ወንዶቹን እየሰለቡ ሴቶቹን ጡታቸውን እየቆረጡ ይበሉታል። ምግባቸውም የሰው ስጋ ነው። ስለዚህ እኛ ነጋዴ ነን፣ ገበሬ ነን ሳትሉ በአንድነት እንዋጋቸው» እያለ ሐሰት የመላበትን ወሬ እየዞረ ይሰብክ ነበር። የሱማሌ ሕዝብም እውነት እየመሰለው ገበሬውም፣ ነጋዴውም ወደ ጣሊያን መጋዘን እየቀረበ ስሙን እያፃፈ፣ ብረት እየተቀበለ ከሊቢያ ወታደሮች ጋር ሆኖ ለውጊያ ተሰለፈ። ይህ ደግሞ ራስ ደስታን በጠላት እጅ እንዲገደሉ አደረጋቸው። እናም ራስ ደስታ ለአንድ ዓመት ያህል ከተዋጉ በኋላ በጠላት ጦር የካቲት 16 ቀን 1929 ዓ.ም እንዲገደሉ ሆነ። ይሁንና ሰማዕትነታቸውን የማይረሳው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስማቸው ይዘከር ዘንድ አዲስ አበባ ውስጥ በስማቸው የሚጠራ ሆስፒታል ሰራላቸው።

«ወዴት ትሄዳላችሁ? እኔ እኮ እዚህ ነኝ» - አርበኛ ከበደች ስዩም

በአገራዊ ሥራ ውስጥ ስልታዊ መንገድ በመቀየስ ሴቶችን ማንም አይችላቸውም። ከእነዚህ እንስቶች መካከል ደግሞ አርበኛዋ ክብርት ወይዘሮ ከበደች ስዩም አንዷ ናቸው። ፋሺስቶች ማይጨው ላይ ባደረጉት ጦርነት በኢትዮጵያ ጦር ላይ ከባድ ጉዳት ካደረሱ በኋላ የወይዘሮ ከበደች ስዩም ባለቤት ደጃዝማች አበራ ካሳንና ወንድማቸውን ገደለባቸው። የወይዘሮ ከበደች ልጅ ዓምደፅዮንም ቢሆን በጠላት እጅ ተይዟል። ይህ መከራ ደግሞ ለእርሳቸው የአገር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የቤተሰብም ሆኗል። እናም ይህንን ያረገዘ ቂማቸውን ለመወጣት የሦስት ወር ነፍሰ ጡር ሆነው ነበር ለውጊያ የወጡት።
የስምንት ዓመት ልጃቸውን አምሃን በመያዝም የቤተሰባቸውን ደም ለመመለስና ለአገራቸው ነፃነት ለመፋለም ወስነው ጥቂት አርበኞችንና አሽከሮችን አስከትለው እያስተባበሩ በእንሳሮ፣ በመርሐ ቤቴ፣ በሚዳና በአካባቢው በመዘዋወር የአርበኝነት ተጋድሏቸውን ጀመሩ። የጠላት እንቅስቃሴ እያሰጋ በመጣበት ወቅትም የአካባቢው ሕዝብ በጠላት የሀሰት ስብከት ተደልሎ ትጥቁን እንዳይፈታና ከትግል እንዳይዘናጋ ከፍተኛ ቅስቀሳ ማድረጉን ተያያዙት። አስቸጋሪውን ወቅት ሱሪ በመታጠቅ ቆላማ ቦታዎችን ይወጣሉ፤ ሸለቆውንም ያቋርጣሉ። «ጥቁር በዚያ ላይ ሴት» ብሎ በድርብ ንቀት የሚመለከታቸውን የፋሺስት ጦር በቁርጠኝነት ለመታገልና እንዲያከብራቸው ለማድረግ። ይህ ደግሞ ተሳክቶላቸው ነበር።
በታላላቅ አርበኞች ሞት ምክንያት ተደናግጠው በዱር በገደሉ የገቡትን ኢትዮጵያዊ አርበኞች ሳይቀር ካሉበት ፈንቅሎ በማደራጀት የሚያህላቸው የሌለው አርበኛዋ ከበደች፤ ግንቦት 25 ቀን 1928 ዓ.ም ሚዳ ወረዳ ቀይ ገደል በተባለው ቦታ ላይ የመጀመሪያ ጦርነታቸውን አድርገው የወገን ጦር የዘመነ መሣሪያ ከታጠቀውና በቁጥር ከሚልቀው የጠላት ጦር ከበባ ሰብሮ እንዲወጣ ያደረጉበት የአመራር ጥበባቸው ዝናቸውን ከፍ አድርጎላቸዋል። በሰኔ ወር 1929 ዓ.ም ደግሞ የአርበኝነት ትግላቸውን በተበታተነ መልኩ የሚከውኑትን አርበኞች ተቀላቅለው በጠላት ላይ በጋራ እንዲሰሩ ይመክሩ ነበር።
በተመሳሳይ አርበኞችን በማስተባበር ጃርሶ ተብሎ በሚጠራው ቦታ የደፈጣ ውጊያ በማድረግ ከጠላት ጎን ተሰልፎ የነበረውን ባንዳና ነጭ ጦር አለቆችን በላቀ ወኔና አመራር ደምስሰዋል። ወልጭ በተባለው ስፍራ ላይም ቢሆን እንዲሁ መሽጎ የአርበኛ ከበደች ስዩምን ጦር እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ ሙከራ ያደረገውን የጠላት ጦር ሽንፈት እንዲከናነብ ያስቻሉ ናቸው።
ሐምሌ 1 ቀን 1929 ዓ.ም ከጣሊያን ጦር ጋር ዱላ ቆርቻ በረሃ ውስጥ ውጊያ የከፈቱት አርበኛዋ ከበደች፤ በወቅቱ ወንድ ልጃቸውን ተገላግለዋል። የወለዱ ሴቶች የሚደረግላቸውን እንክብካቤ በወቅቱ ያላዩት አርበኛዋ የአራስነት ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ በአንዲት ጎጆ ውስጥ እንዲገቡ ቢደረግም በጎጆዋ ላይ የቦምብ ናዳ ይወርድባት ነበር። እናት አርበኛዋ ከበደች ስዩም ግን የአራስ ወገባቸው ሳይጠና ለቀጣይ ትግልና ውጊያ ጨቅላ ልጃቸውን ይዘው ከሸዋ በመነሳት ወደ ወለጋ ሄደዋል።
አንድ ጊዜ ጎጃም ቡሬ ዳሞት ውስጥ አርበኛዋ የሚመሩት ጦር በጠላት ጦር ጥቃት ተከፍቶበት የወገን ጦር ማፈግፈግ ሲጀምር እንዲመለስና እንዲበረታ ለማድረግ አርበኛ ከበደች ስዩም እንዲህ እንዳሉ ይነገርላቸዋል። «ወዴት ትሄዳላችሁ፤ እኔ እኮ እዚህ ነኝ» ችግር ውስጥ ቢሆኑም አርበኞችን ከማበርታት ያልተቆጠቡት ወይዘሮ ከበደች፤ በሸዋ፣ በወለጋና በጎጃም የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ለእናት አገራቸው ነፃነት ታግለዋል። ይህ አኩሪ ተግባራቸው ደግሞ አምስት ከፍተኛ የክብር ኒሻኖችን አሸልሟቸዋል። ግን ከሞት የሚቀር የለምና በታኅሣሥ ወር 1971 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

አብዲሳ አጋ - የ14 ዓመቱ ዘማች


ኮሎኔል አብዲሳ አጋ በ1928 ዓ.ም በጣሊያን ወረራ ወቅት ተማርከው ወደ ጣሊያን ከተወሰዱ አርበኞች መካከል አንዱ ሲሆኑ፤ በጣሊያን አገር ብርድ ልብሳቸውን ቀዳደው በመቀጣጠል በመስኮት አምልጠው በመውጣት በርካታ ጀግንነቶችን የፈጸሙ ኢትዮጵያዊ ወታደር ናቸው። ኮሎኔል አብዲሳ አጋ የተወለዱት በ1912 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞን ሲሆን፤ በ12 ዓመታቸው አባታቸው በንዴት ወንድማቸውን በመግደላቸው ሲታሰሩ አባታቸውን ለማስፈታት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ቢያደርጉም ሳይሳካ በሞት ተለዩዋቸው። ይህ ቁጭት ደግሞ በ14 ዓመታቸው የኢትዮጵያን ጦር ለመቀላቀል አስደፈራቸው።
ኮሎኔል አብዲሳ ጦሩን ከተቀላቀሉ ከሁለት ዓመት በኋላ የአደዋን ሽንፈት ለመበቀል የዛተው ፋሺስት ሞሶሎኒ በድጋሚ ኢትዮጵያን ሲወር አገራቸውን ለመከላከል በ16ዓመታቸው ወራሪውን ጦር መዋጋት ጀምረዋል። ውጊያ ላይ ባጋጠማቸው የመቁሰል አደጋም ህክምና ቢደረግላቸውም ቆይታቸው ግን በቁም እስር ውስጥ ነበርና ህመማቸው በረታ። ከዚያም አልፎ ከሌሎች 37 የሚሆኑ የቁም እስረኞች ጋር ተጠርጣሪ ተብለው በከባድ ስቃይ ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ሆነ። ከዚያም የጣሊያን ግዛት በነበረችው በሶማሊያ በኩል ወደ ጣሊያን ተወስደው በሲሲሊ ደሴት በሚገኝ ማረሚያ ቤት እስረኛ ተደረጉ።


አልሸነፍ ባይነት መለያቸው የሆነው ኮሎኔል አብዲሳ ሁሊዮ ከተባለ ዩጎዝላቪያዊ የጦር እስረኛ ጋር በመተባበር ከባድ ጥበቃ ከሚደረግበት ማረሚያ ቤት ለማምለጥ ስልት ይቀይሱ ጀመር። ለስኬታቸውም ይበጃቸው ዘንድ የብርድ-ልብስ ተጠቀሙ። ቀዳደው በመቀጣጠልም በመስኮት በኩል አመለጡ። ከዚያ በኋላ ግን ሽሽት አልገጠማቸውም። ይልቁንም በማታ ወደ ማረሚያ ቤቱ በመመለስ ጠባቂዎቹ ላይ ጥቃት በመፈጸም እስረኞቹን ነፃ ማውጣት ችለዋል። ያመለጡት እስረኞች ደግሞ ከእስር ቤቱ ጠባቂዎች በወሰዱት መሣሪያ በመታገዝ የአማጽያን ጦር ያደራጁ ሲሆን፤ ጦሩን እንዲመራም የመረጡት ጀግናውን ኮሎኔል አብዲሳን ሆነ።


የተለያዩ የጣሊያን ወታደራዊ ሠፈራዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም ወራሪዎቹ ጣሊያኖች ኢትዮጵያ ውስጥ ከነበረው የአርበኛ እንቅስቃሴ ያልተናነሰ ጥቃት በሀገራቸው ያጋጥማቸው ጀመር። በኮሎኔል አብዲሳ ጦር እጅግ የተረበሹት ጣሊያኖችም በርካታ ስጦታዎችን ቃል በመግባት ውጊያውን እንዲያቆሙ እና የእነሱን ጦር እንዲቀላቀል ለመኗቸው። እርሳቸው ግን ከፋሺስት ሥርዓት ጎን እንደማይ ቆሙ በማስረገጥ ጥያቄውን ውድቅ አደረጉት።


በወቅቱ እየተጋጋለ የመጣው የጀርመን ናዚ ሥርዓት ሁለተኛው የዓለም ጦርነትን ሲጀምር ፋሺስት ሙሶሎኒ ደግሞ ከጀርመኖች ጋር አብሯል። በተመሳሳይ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና አሜሪካን ጨምሮ በርካታ የምዕራብ አገሮች የሕብረት ጦር መስርተው የሙሶሎኒን ጦር መውጋትን አልመዋል። ይህ የሕብረት ጦር የኮሎኔል አብዲሳን ዝና በመስማቱ ጣሊያንን ለማዳከም ለኮሎኔል አብዲሳ ጦር የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ። በድጋፉ መጠናከር ፋሺስቱን ሠራዊት ማርበድበድ የቀጠሉት ኮሎኔል አብዲሳም የጣሊያን ጦር ተሸንፎ ዋና ከተማዋ ሮም በአሜሪካን እና እንግሊዝ እንድትመራ አደረጉ። ይህ ደግሞ ኃያልነታቸውን አስመሰከረላ ቸው፤ ከተለያዩ አገር የወጡ ወታደሮችን በሙሉ ክንዳቸው ላይ የኢትዮጵያን ባንዲራ እንዲያስሩ በማድረግም የአገራቸው ባንዲራ እንዲውለበለብ ዕድል ሰጣቸውም። ሮም ከተማ ሲገቡ ደግሞ በዓለም አቀፉ ህብረት ጦር ትልቅ አቀባበል እንዲ ደረግላቸው የሆነውም ጥንካሬያቸው አይሎ ስለነበር ነው።


ከተጨማሪ ወታደሮች ጋር በዓለም አቀፉ ህብረት ስር የሚመራ ጦር መሪ በመሆን ጀርመንን ለማሸነፍ በሚደረገው የመጨረሻ ውጊያ ላይ የተሳተፉት ኮሎኔል አብዲሳ፤ የኢትዮጵያን ባንዲራ ከእጃቸው ሳይለዩ በርካታ የጀርመን ከተሞችን ነፃ ማውጣት ችለዋል። ከጦርነቱ መገባደድ በኋላም የእንግሊዝ፣ የካናዳ እና የአሜሪካ መንግሥታት ጦራቸውን ተቀላቅለው እንዲቀጥሉ በርካታ ጥቅማ ጥቅሞችን ቢያቀርቡላቸውም «ኢትዮጵያ ምንም ያህል ድሃ ብትሆንም ዜጋዋ ሕዝቡን እና መንግሥቱን ጥሎ አይሄድም» በማለት አረጋግጠው ጥያቄውን ሳይቀበሉ ቀሩ።


ተቀላቀለን የሚለውን ጥያቄ ውድቅ መሆኑ ያልተዋጠላቸው አንዳንድ የሕብረት ጦር አባላት በወንጀል ከሰው ማረሚያ ቤት አስገቧቸው። ሆኖም እስሩ ወደ ገንዘብ ቅጣት ተቀይሮላቸው ገንዘቡን በመክፈል በነፃነት ወደ አገራቸው መመለስ ችለዋል። በዚህም ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በክብር ተቀብለዋቸው የመከላከያ ሚኒስትር ወደ ነበሩት ራስ አበበ አረጋይ መርተዋቸዋል። እርሳቸውም እንደታዘዙት ኮሎኔል አብዲሳን ወደ ሆለታ ወታደራዊ ሠፈር እንዲገቡ አደረጓቸው።


ኮሎኔል አብዲሳ አነስ ባለ ወታደራዊ ቦታ የተወሰነ ጊዜ አገለገሉ። ነገር ግን ለጉብኝት የመጡ የውጭ ሀገር የጦር መሪዎች ስለ ዝናቸው ሲያወሩ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጆሮ ደረሰ። በዚህም ወደ ቤተ መንግሥታቸው በማምጣት በኮሎኔልነት ማዕረግ የንጉሡ ጠባቂ እንዲሆኑ አድርገው ሾሟቸው። እስከ ንጉሣዊ ሥርዓቱ መውደቅ ድረስም በቦታው ሰሩ። ይሁንና ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። እንግዲህ ኢትዮጵያ እንዲህ ያሉና ሰማዕትነትን የማይፈሩ ተጋድሏቸው ወሰን የሌለው ልጆች ባለቤት መሆኗን በጥቂቶቹ አርበኞች መረዳት ይቻላል። ይህ ዋጋም በዓለሙ ምድር ነፃነቷን የማታስነካ አገር እንዳለች አስገንዝቧል። ይህን የማስቀጠሉ ጉዳይ ደግሞ የዛሬው ትውልድ መሆኑን አበክረን እየተናገርን ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለኢትዮጵያ አርበኞች ይሁን! አልን።

 

ጽጌረዳ ጫንያለው

 

Published in ማህበራዊ
Sunday, 06 May 2018 03:26

«ወዴት እያመራን ነው?»

ፀሐይ ብርሃንዋን ለመሸሸግ ቀይ ግምጃዋን በደማቁ ዘርግታለች:: በስራ እና በተለያዩ ምክንያቶች ደፋ ቀና ሲል የዋለው ለፍቶ አደር ከቤቱ ለመግባት ይጣደፋል:: አቅም ያለው ታክሲ ለመያዝ ዕጅ ያጠረው ደግሞ አውቶቡስና ሌዎንችና ፍለጋ ይጋፋል:: እኔም ከዋልኩበት ወደ ቤቴ ለመግባት ከጨለማው ጋር እሩጫዬን ተያይⶴዋለሁ፡፡ ቤቴ ከመድረሴ በፊት ግን ፀሐይዋ ተራውን ለጨለማ አስረከበች፡፡ እየተጣደፍኩ ሰፈር ስደርስ ያጋጠመኝ ግን አስፈሪም አሳሳቢም ነበር፡፡ ከቅረብ ጊዜ ወዲህ ገርጂ (ወረገኑ) አዳዲስ ነገሮች መታየት መጀመሩን ብረዳም ሁኔታው መበባሱ የታወቀኝ የዚያን ቀን ምሽት ነበር፡፡
ገርጂ (ወረገኑ) ከጥቂት ዓመታት በፊት በፀጥታ በኩል ምንም ችግር አልነበረም፡፡ አዛውንቱ ወጣቱ ሴቶች ሳይቀሩ በሰላም ወጥተው በሰላም የሚገቡበት ከየትኛውም የአዲስ አበባ አካባቢ እግር ጥሎት በአካባቢው ቢዘዋወር አንዳችም ነገር አይገጥመውም ነበር፡፡ ሰፈሩ አዲስ በመሆኑ በማህበራዊ ኑሮ ረገድ ጥሩ መተሳሰብ የሚታይበት ነው፡፡ ቤቶቹ በማህበር የተሰሩ በመሆናቸው ሁሉም ነዋሪ ያለስጋት የራሱን በር ዘግቶ ይወጣል በሰላምም ከፍቶ ይገባል፡፡ የሆነ ችግር ሲከሰት ግን በሮች ሁሉ ይከፈታሉ፡፡ ችግሮቹም እንደ ክብደታቸው በህበረት ይከናወናሉ፡፡ የሰፈሩ ማህበራዊ መስተጋብር ለሌሎችም ዓርዓያ ሊሆን የሚችል ነው፡፡ ነገር ግን በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል እንዲሉ ገርጂ ዛሬ የቀድሞ ስሟ እየተለወጠ ነው፡፡ ወንዶች ጨለምለም ካለ በስጋት የሚንቀሳቀሱበት ሴቶች ንብረቶቻቸውን የሚዘረፉበት አቅመ ደካማዎች የሚዋከቡበት በአጠቃላይ አካባቢው ሰላም የታጣበት ሆኗል፡፡ እስከ አሁን ባለኝ መረጃ የድርጊቱ ተዋናዮች የአካባቢው ወጣቶች ሳይሆኑ በትውውቅና በዚህ የወንጀል ድርጊት ከሩቅ ሰፈር የሚመጡ ናቸው፡፡
እንደዚህ የመሳሰሉት ማህበራዊ ጠንቆችን አስቀድሞ ለመከላከል ነዋሪው ህብረትሰብ በየማህበሩ የአካባቢውን ጸጥታ ሊያስክበሩ የሚችሉ ጥበቃዎችን ቢቀጥሩም ችግሩ ሊወገድ አልተቻለም፡፡ ጥበቃዎቹ ለጥቂት ደቂቃዎች ፊታቸውን አስመትተው የት እንደሚገቡ አይታወቅም፡፡ ኗዋሪው የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት በሚገናኙበት መድረክ ሁሉ የጉዳዩን አስከፊ ገጽታ በማንሳት መወያየቱ አልቀረም፡፡ መፍትሄ ግን የለም፡፡ ችግሩ አድማሱን በማስፋት ጨለማን ተገን ያደረጉት እነዚህ ዘራፊዎች አጥር ዘለው ግቢ በመግባት ግቢ ውስጥ የተረሱ ቁሳቁሶችን ጠራርገው ይወስዳሉ፡፡ ሁኔታው ከመቼውም በበለጠ እየተባባሰ መጥቶ የቤት በሮችን ሰብረው በመግባት ከባድ ወንጀል ወደመፈፀም ሙከራ እየተሸጋገረ ነው። በሰፈሩ አንዳንድ አካባቢዎችም ይህ ድርጊት ይፈጸማል፡፡
እነዚህ ማህበራዊ ችግሮች ሌላም ይዘውት የመጡት አስከፊና እጅግ አሳሳቢ ችግር አለ፡፡ እሱም የምሽት ጭፈራ ቤት መስፋፋት ነው፡፡ ከዚህ በፊት በሰፈሩ እምብዛም የተለመዱ የምሽት ጭፈራ ቤቶች ናቸው፡፡ እነዚህ መዝናኛ ቤቶች ደግሞ የወንጀለኞች መሸሸጊያ በመሆን ሰፈሩን እያመሱት ነው፡፡ ዜጎች በፈለጉት የስራ መስክ ተሰማርተው ኑሯቸውን ቢመሩ ክፋት የለውም፡፡ ነገር ግን በተለይ እንደ ምሽት ክበቦች ያሉ የንግድ ቤቶች በመኖሪያ ሰፈሮች መስፋፋታቸው ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበዛል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በገርጂም እየተከሰተ ያለው አሳሳቢ ነገር በዋንኛነት ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ብዙዎች የወንጅል ተሳታፊዎች በጉልበት ከህዝቡ የዘረፉትን ገንዘብ የሚጨፍሩበት በነዚህ ዳንኪራ ቤቶች ነው፡፡ እነዚህ ከማህበረሰባችን ባህልና ልማድ ጋር ፈጽሞ የማይገናኙ መጤ የባህል ወረራዎች በተለያየ መንገድ የህብረተሰቡን ባህላዊ እሴቶች እየሸረሸሩት ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን ከምንታወቅባቸዉ አኩሪ ባህሎቻችን መካከል እንደየ እምነቶቻችን ዝሙት እና ከዚህ ጋር ተያያዥ የሆኑ አስነዋሪ ድርጊቶችን መጠየፍ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን እንኳን ሊተገበሩ ቀርቶ ለጆሮ የሚቀፉ ተግባሮችን እያየን ነው፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በመዲናይቱ በአንዳንድ አካባቢዎች የምሽት ጭፈራ ቤቶች መረን በለቀቀ ሁኔታ እንደ እንጉዳይ እየፈሉ ነው ብል አላጋንኩም፡፡ ሰፈራችን ያሉትን የምሽት ክበቦች ዳግማዊ “ ቺቺንያ” እስከ ማለት ተደርሷል፡፡
ገርጂ( ወረገኑ) የአካባቢው የቀድሞ ስም ነው፡፡ በዚህ ሰፈር ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ የሙዚቃ ጩኸት እንኳን በስራ የደከመን አዕምሮን ማሳረፍ ቀርቶ ለደቂቃ መቀመጥ አያስችልም፡፡ ከሙዚቃው ጩኸት በተጨማሪ በጭፈራ ቤቱ ለመዝናናት የተገኙት ሰዎች ሁኔታ ለጉድ ነው፡፡ በአጋጣሚ የኔ የመኖሪያ ቤት ለጭፈራ ቤቶች ቅርብ በመሆኑ የችግሩ ሰለባ ከሆኑት መካከል አንዱ ነኝ፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ የምሽት ክበቦችን መክፈት እንደ ማይቻል አውቃለሁ፡፡ ይህን የሚከለክል በህግ የተቀመጠ አስገዳጅ ሁኔታ ይኑር አይኑር መረጃ ግን የለኝም፡፡ ነገር ግን ለነዚህ ስራ በተመረጡ አካባቢዎች የምሽት ክበቦችን ከፍቶ መሰራት ክልክል አልነበረም፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት ገርጂ ያለምንም ማጋነን ከሶስት መኖሪያ ቤቶቸ አንዱ ፔንሲዮን ነው፡፡ እነዚህን የመሰሉ መረን የለቀቁ እንቅስቃሴዎችን እስካሁን ምንም ዓይነት መድሃኒት ካለተገኘለት ለኤች ኤይ ቪ ኤድስ መስፋፋት አይነተኛዉ መንገድ ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት በመንግስትና በህዝቡ ያላሰለሰ የነቃ ተሳትፎ የወረርሺኙ ስርጭት(የስርጭት መጠኑ) ቀንሶ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ዳሩ ግን በአሁኑ ወቅት በወጣቱ መዘናጋትና ትኩረት ማነስ በሽታው(የቫይረሱ ስርጭት) እንደገና በማገርሸት በርካታ ወገኖችን እየጎዳ ነው፡፡ ለበሸታው(ለቫይረሱ ስርጭት) እንደገና ማንሰራራት ደግሞ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካል ችላ ባይነትና ወጣቱም ኤድስ ጠፍቷል በሚል መዘናጋት የተፈጠረ ችግር ነው ፡፡ ወረርሽኙ በጣም በተጋነነበት በሰማንያዎቹ(በአስራ ዘጠኝ ሰማኔያዎቹ) አካባቢዎች ወሬው ሁሉ ስለበሸታዉ(ኤድስ) ገዳይነት እና አስከፊነት በመሆኑ በሁሉም ዘንድ መደናገጥ ተፈጥሮ ነበር፡፡ “መቆጠብ፤ መወሰን እና መጠቀም ” የሚባሉት (የኤች አይቪ ኤድስ) የኤድስ መርሆች ዛሬ ከቁብ የሚቆጥራቸው የለም፡፡ እውነቱን ግልፅ ለማድረግ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሽታው (ቫይረሱ) ከምድረ ገጽ የጠፋ ይመስል “አስርሽ ምቺው” በስፋት መታየቱ የመዘናጋቱ ስፋት ጫፍ መድረሱን አመላካች ነው፡፡ እነ "ሹገር ዳዲ እና ማሚን" በምሽት ጭፈራ ቤቶች ማየት አዲስ ነገር አልነበረም፡፡ በጣም የሚያስገርመው መካሪ ሊሆኑ የሚችሉ አዛውንቶች የድርጊቱ ተዋናይ መሆናቸው ነው፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ቢያንስ በጎልማሳ የዕድሜ ክልል የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስለ በሽታው አስከፊ ጎን በማንሳት ውይይት ያደርጉ እንደ ነበር ትዝታው አለኝ፡፡ አንዳንዶችንም በቀጥታ በጉዳዩ በመሳተፍ የበኩላችንን አስተዋፅኦ አድርገናል፡፡ ይሁን እና በከፍተኛ ውጣ ውረድ በመጠኑ ጋብ ብሎ የነበረው ወረርሽኝ ባሁኑ ጊዜ በአስደንጋጭ ሁኔታ ለመስፋፋቱ ምቹ ሁኔታ የተፈጠረለት ይመስላል በርካታ እንስቶች በየመኖሪያ ቤቱ አጥር ስር ተኮልኩለው ለተመለከተ “ወዴት እያመራን ነው?” ያስብላል፡፡ በሽታው ያደረሰው ጠባሳ ገና ሳይጠፋ ወጣቱ ክፍል ለሌላ ዙር እልቂት ራሱን እያዘጋጀ እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡ የእኛው ሰፈር ገርጂም የበሽታው ስርጭት እምብርት ከመሆን የሚያመለጥ አይመሰለኝም፡፡ ለበሽታው መስፋፋት ደግሞ ከአሁን በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በየሰፈሩ በመስፋፋት ላይ የሚገኙት ፔኒሲዮኖች ናቸው፡፡ፔኒሲዎኖቹ ቢያንስ በቀን ከ10ያላነሱ ዝሙት ፈፃሚዎችን ያስተናግዳሉ፡፡
ከዝሙት ተዋናዮቹ መካከል ተማሪዎች ባለትዳሮች፤ ትዳር የለሾች እና ሌሎችም የህበረትሰብ አካላት ይገኙበታል፡፡ በጣም አሳዛኙ ነገር ደግሞ ፔንሲዮኖች ያለገደብ ሲስፋፉ በቀበሌው የሚገኙ ጉዳዩ የሚመ ለከታቸው መሥሪያ ቤቶች እንዳላየ ችላ ማለታቸው ነው፡፡ ሲጀመር በሽታው (የቫይረሱ ስርጭት) እንደገና ማገርሸቱ (ማንሰራራቱ) እየታየ ፔንሲዎን ከፍተው ለሚሰሩ ነጋዴዎች ፈቃድ መስጠቱ ነው፡፡ ፈቃድ መስጠቱ ብቻ አይደለም ችግሩ አሳሳቢ መሆኑ እንዳይታወቅ የእርምት እርምጃ አለመወሰዱ ነው፡፡ በሽታው(ቫይረሱ) በዋናነት እያጠቃ ያለው አምራቹን ሀይል በመሆኑ በግልፅ እየታወቀ ለምን ትኩረት እንደተነፈገው ለእኔ ገልፅ አይደለም ፡፡
ወረርሽኙ በአሁኑ ወቅት በመላ ዓለም ዘር ሃይማኖት ሳይመርጥ መላውን የሰው ዘር ህይወት ከማጥፋቱም በላይ የከፋ ማህበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ድቀት እያደረሰ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሳህራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ባደረጉት ያለሰለሰ ጥረት አበረታች ውጤት መመዝገቡ እውነት ቢሆንም ታጥቦ ጭቃ የመሆኑ ጉዳይ ግን አነጋጋሪ ይመስለኛል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በማደግ ላይ ያሉ ሃገራትን በአሁኑ ወቅት ዋነኛ ችግራቸው ከድህነት እና ኋላ ቀርነት ለመላቀቅ ደፋ ቀና በሚሉበት ወቅት ተመናምኖና እንዲያውም ተዳክሞ የነበረው የጤና ችግር እንደገና ማንሰራራቱ ሁሉንም ወገን ሊያሳስበው ይገባል፡፡ መንግስትዊ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ባለድርሻ አካላትና(ሚዲያዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ኤች አይቪ በደማቸው የሚገኝ ወገኖች ማህበራትና ጥምረቶች፣ አጋር ድርጅቶች፣ አመራሩና) በአጠቃላይ ህበረተሰቡ ችግሩ ችግሬ ነው በማለት መላ ሊፈልግለት (ማህበራዊ ሀላፊነታቸውን ሊወጡ) ይገባል፡፡ በተለይ ደግሞ ከጉዳዩ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው አካላት ከምንጊዜውም የበለጠ ተግተው ሊሰሩ ይገባል፡፡

ገላውድዮስ ከገርጂ

Published in አጀንዳ

ኢትዮጵያዊያን በምንም መልኩ ሽንፈትን ተቀብለው አያውቁም። በአገራቸው ጉዳይ ሰላም ካልተሰማቸው ተኝተው አያድሩም። በቅድሚያ ለሰላም ጊዜ ይሰጡ ይሆናል እንጂ በሉዓላዊነታቸው መቼም አይደራደሩም፡፡ በነፃነታቸው መደራደርን መቼም አይፈልጉትም። በመሆኑም ባልሰለጠነው መሳሪያ ሳይቀር ህይወታቸው ከአገር ነፃነት አይበልጥም በማለት በክቡር መስዋዕትነታቸው ክቡር ሃገር አስረክበውናል፡፡
የኢትዮጵያዊያንን የዓድዋ ድል አምኖ መቀበል ያቃታት ሃገረ ጣሊያን ከአርባ ዓመታት በኋላ በ1928 ዓ.ም ዳግም ኢትዮጵያን ወረረች። በዚህም ወቅት ለአምስት ዓመታት በሃገራችን ብትቆይም በአርበኞች ትግል የተረጋጋ አገዛዝ ማስፈን አልቻለችም፡፡ ዳግም የኢትዮጵያዊን የድል በትር ቀምሳ ከአምስት ዓመታት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ሽንፈት ተከናንባለች፡፡ የዛሬ 77 ዓመት ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም፡፡
ይህ ድል ለኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ ትርጉም ያለው ድል ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በየትኛውም ጊዜና ሁኔታ ለውጭ ወረራ የማይንበረከኩና የማይበገሩ ህዝቦች መሆናቸውን ለዓለም ማህበረሰብ ያስመሰከረ ድል ነው፡፡ ለትውልድም የሉዓላዊነትና ነፃነት አስፈላጊነትን በደምና በአጥንት የማስከበር ጽናትና ወኔ ያሰነቀ ድል ነው፡፡
ከዓድዋም ሆነ ከሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ድል ይህ ትውልድ ብዙ ትምህርት ሊወስድ ይገባል፡፡ የዛሬው ትውልድ ጦር ሰብቆ ሉዓላዊነቱንና ነፃነቱን የሚቀማው ኃይል ባይኖርም ድህነት የሚባል ትልቅ ጠላት ግን ከፊቱ ተደቅኖ ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ በደምና በአጥንት ለጸናው ሉዓላዊነታችን ፈተና መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ አሁን የኢኮኖሚ ዕድገትና ሉዓላዊነት ያስፈልገናል፡፡ ከዓለም አገራት ጋር የሚኖረን ግንኙነት በንግድና ኢንቨስትመንት እንጂ በዕርዳታና ልመና ላይ የተመሰረተ መሆን የለበትም፡፡ ስለሆም የአሁኑ ትውልድ የፀረ ድህነት ትግሉን በድል መወጣት ወቅቱ የሚጠይቀው የትግል ስልት ነው፡፡
77ኛውን የድል በዓል ስናከብርም የአባቶቻችን አንፀባራቂ ድልና ታሪክ ተዳፍኖ እንዳይቀርና ተተኪው ትውልድም ድሉን በፀረ ድህነት ትግሉ እንዲደግመው ቃል በመግባት መሆን አለበት፡፡ የዘመኑ ጀግንነት የሚለካው ከድህነት በመውጣት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከዚህ ትውልድ ይጠበቃል፡፡
ወጣቱ ትውልድ 77ውኛን የአርበኞች ድል በዓል ሲያከብር ታሪክ ነጋሪ ብቻ ሳይሆን ታሪክ ሠሪም መሆኑን በማሳየት መሆን አለበት። በመሆኑም ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት፣ ለሚያነሳቸው ሃሳቦች ምክንያታዊ በመሆን፣ በመልካም ስነምግባር በመታነፅ እንዲሁም የሥራ ባህሉን በማሳደግና ለሥራ በመትጋት የአባቶቹን የድል ታሪክ በአዲስ መልኩ መድገም አለበት፡፡ ይህንን ለማድረግ በሀገር ፍቅር ስሜት በደም የተጻፈውን ታሪክ በኢኮኖሚ ሉዓላዊ የሆነች አገር በመገንባት ጊዜውን፣ እውቀቱንና ጉልበቱን መስዋዕት በማድረግ ገቢውን በማሳደግ ለኢኮኖሚ ዕድገቱ የድርሻውን መወጣት አለበት፡፡
የሃገራችን ቀደምት ትውልዶች የውጭ ጠላትን አሳፍረው ሃገራችንን አስከብረዋል፡፡ ይህ ለአሁኑ ትውልድ የኩራት ምንጭ ነው፡፡ ለመጪው ትውልድ ድህነትን ሳይሆን ብልጽግናን፤ መከፋፈልን ሳይሆን አንድነትን፤ ሁከትና ብጥብጥን ሳይሆን ሰላምን ማስተላለፍ አለበት። የዛሬው ትውልድም ይህንን ድል ከተጎናጸፈ ቀጣዩ ትውልድ በጀግንነት ሲዘክረው ይኖራል፡፡
ልክ አባት አርበኞችና እናት አርበኞች በውጭ ወራሪ መሸነፍ ሰላም እንደማይሰጥ አምነው በዱር በገድል በአርበኝነት ታግለው ለድል እንደበቁት ሁሉ፣ የዛሬው ትውልድ ደግሞ ድህነት እንቅልፍና ሰላም የሚነሳ ችግር መሆኑን ተረድቶ ድህነትን ድል ለማድረግ መረባረብ ይጠበቅበታል፡፡ ይህንን ተግባር በድል ለመወጣትም አንድነቱን ሊያጠናክር ይገባል። ጀግኖች አባቶቻችን የውጭ ወራሪዎቹን ድል መንሳት የቻሉት ብዙ ሆነው እንደ አንድ በመሰለፋቸው መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው፡፡
ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ሁነቶችና አስተሳሰቦችን በመከወን አርበኞቻችን ያበሩትን የድል መብራት መከተል፤ የማይጠፋ ችቧቸውን በማንቦግቦግ በድህነት ላይ ደማቅ ድል መጎናፀፍ ይቻላል፡፡ለፀረ ድህነት ትግል ድል ፋና ወጊ በእጃችን አለ፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ
Sunday, 06 May 2018 03:22

የአሸናፊነት ተምሳሌት

ወደ አራት ኪሎ የድል ሐውልት የሚወስዱ መንገዶች በአራቱም ማዕዘን ግራና ቀኝ የሚታየው በተለያየ አልባሳት የደመቁ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ እንደ ወትሮው የተሽከርካሪ ትርምስና ጩኸት የለም፡፡ በየአቅጣጫው የሚሰማው አባት አርበኞችን የሚያወድስ ህብረ ዝማሬ ነው፡፡ እዚህ ጋ ለነፃነት የተጋደሉ ጀግኖችን ፎቶ የያዘ ቲሸርት የለበሱ ወጣቶች በቡድን ቡድን ሆነው ህብረ ዝማሬ ያሰማሉ፡፡ እዚያ ጋ ደግሞ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን አልባሳት የለበሱ ወጣቶች የጀግኖችን ስም እየጠሩ፣ እንደ አባቶቻቸው ጦር እየሰበቁ ይፎካራሉ፡፡ ወደ አደባባዩ ውስጥ ጠጋ ስንል ደግሞ ገና የአርበኝነት ወኔያቸው ያልለቀቃቸው አርበኞች ጦራቸውን እየሰበቁ ሲፎክሩ ይታያል፡፡ 

ኢትዮጵያውያን አርበኞች ፋሺስት ጣሊያን ከአገራቸው ያባረሩበትን 77ኛውን የአርበኞች ድል መታሰቢያ ለመዘከር ገና ከማለዳው ጀምሮ ዙሪያውን በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ደምቆ የነበረው የአራት ኪሎ የድል ሐውልት አደባባይ እየረፈደ ሲሄድ በአራቱም አቅጣጫ መፈናፈኛ አልነበረውም፡፡ በአደባባዩ ላይ ያለውን ትዕይንት ለማየት ዳርዳሩን ያሉ ወጣቶች አንዱ በአንዱ ትክሻ ላይ ሲንጠራሩ ይታያል፡፡ የአባት አርበኞች ሽለላና ፉከራ ቀልባቸውን ሲስበው በየደረጃውና በአካባቢው ባለው የብረት ድልድይ ላይ ሆነው የሚመለከቱ ወጣቶች በወኔ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ከአባቶች ጋር ይፎክሩ ነበር፡፡ ከትምህርት ቤቶች፣ ከተለያዩ ክበባትና ማህበራት በቡድን የመጡ ወጣቶችም ለበዓሉ ከፍተኛ ድምቀት ሰጥተውታል፡፡
አንዲት ወጣት ግጥም ልታቀርብ ወደ መድረኩ ተጋበዘች፡፡ መድረኩ ላይ እንደወጣችም  በሽለላ ዜማ የጀግኖችን ስም እየጠራች ግጥሟን ጀመረች፡፡ ይህኔ ነበር የአባት አርበኞች ስሜት ገንፍሎ መድረኩን ፉከራ በፉከራ ያደረገው፡፡ የልጅቷ ግጥም ለጊዜውም ቢሆን ቆም አለ፤ ምክንያቱም በሽለላ ዜማ የጀመረችው ግጥም አንድም አባት አርበኛ እንዲቀመጥ አላስቻለም፡፡ ወደቦታቸው ሲቀመጡ በምርኩዝ የሄዱት አባት አርበኞች ወኔያቸው ሲቀሰቀስ ምርኩዙ ምርኩዝ መሆኑ ቀረና እንደ ጦር እየሰበቁ መፎከሪያ አደረጉት፡፡ ጸጉራቸው ነጭ ብቻ የሆነና ሰውነታቸው በእርጅና የተጎዳ የሚመስሉ አርበኞች እንደዚያ ሲሽከረከሩ ያየ የራሱም ወኔ ይተናነቀዋል፡፡ ከርቀት ሆነው የሚከታተሉ ሁሉ ባሉበት ሲፎክሩና ሞራል ሲሰጡ ይሰማል፡፡ በአባቶች ፉከራ ታጅቦ የልጅቷ ግጥም ግማሹ እየተሰማ ግማሹም በፉከራ እየተዋጠ አለቀ፡፡
ወጣት ሳምሶን አለማየሁ ይህን ትዕይንት ከተከታተሉ ወጣቶች አንዱ ነው፡፡ ሳምሶን እንደሚለው ታሪካዊ በዓላት በእንዲህ ዓይነት ዝግጅት መከበራቸው በወጣቶች ዘንድ መነቃቃት ይፈጥራል፡፡ በተለይም የአራት ኪሎ የድል ሐውልት አደባባይ ብዙ ወጣቶች የሚታዩበትና ታሪካዊ ቦታ ነው፡፡ ቢያንስ በዚህ አካባቢ ያለፈ ወጣት እንኳን «ይሄ ምንድነው» ብሎ መጠየቁ አይቀርም፤ የአርበኞች ቀን ማለት ወራሪው ፋሽስት ጣሊያን ከኢትዮጵያ ተጠራርጎ የወጣበት ቀን መሆኑን ያውቃል፡፡ ለታሪክና ለአገር ፍቅር መነሳሳትን ይፈጥራል፡፡
እንዲህ ዓይነት ታሪካዊ በዓላት በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ትኩረት እየተሰጣቸው እንደሆነ ያስተዋለው ወጣት ሳምሶን፣ አንድ የታዘበው ነገር እንዳለም ይናገራል፡፡ አባት አርበኞች «ለጠላት አንንበረከክም» ብለው አገሪቱን ከነክብሯ አስረክበዋል፡፡ ባህሏና ቋንቋዋ በውጭ ወራሪ ሳይበረዝ ያስረከቧትን አገር አሁን አሁን ወጣቱ ላይ በውጭ ፋሽን መወረሩ ሌላኛው ቅኝ መገዛት እንዳይሆን ይፈራል፡፡ «ይህን የድል በዓል ለማክበር ድንቅ የሆኑ የአለባበስ ውበት፣ የራሳችን ቋንቋ እያለን የውጭ ፋሽን አድናቂ መሆናችን ሊስተካከል ይገባል» ሲል ያሳስባል፡፡
ተማሪ ዘሪሁን ተሾመ በዓሉን ለማክበር ከመጡት መካከል አንዱ ነው፡፡ እርሱ እንደሚለው፣ ይህን በዓል ለማክበር በህብረ ዝማሬ፣ በመጣጥፍና መፈክሮችን በማዘጋጀት ሂደት ውስጥ ብዙ ነገር እንዲያውቅ አድርጎታል፡፡ እንዲህ ዓይነት በዓላት በተማሪዎች እንዲዘጋጁ መደረጉም በዓሉን እንዲያውቁት ያደርጋል፤ ስለአገራቸው ታሪክ እርስበርስ እንዲወያዩና የአባቶቻቸውን ወኔ በመቅሰም የአሸናፊነት ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡
ወኔ ውስጣቸውን እየቀሰቀሰው ጦራቸውን እየሰበቁ ሲፎክሩ ወደነበሩት አንድ አባት አርበኛ ጠጋ አልኩ፡፡ አባት አርበኛ በጋሻው ቴሶ ይባላሉ፡፡ በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ጊዜ የስምንት ዓመት ታዳጊ ነበሩ፡፡ በዚህ ዕድሜያቸው ጫካ ገብተው ነበር፡፡ ቀን ቀን ጫካ ውስጥ ተደብቀው በመዋል ማታ ማታ ወደቤት ይገባሉ፡፡ በዚህ ሁነት ውስጥ የነበረውን የውስጥ አርበኞችና የባንዳዎች ሁኔታ ያስታውሳሉ፡፡ ባንዳዎች እየሸሹ ሲሄዱ የጣሉትን መሣሪያም እያነሱ ይወስዱ ነበር፡፡
የውስጥ አርበኞች የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀሙ ነበር፡፡ የፋሽስት ጣሊያን ወራሪ እየመጣ ከሆነ ማሽላ ጠባቂ መስለው «ዝንጀሮ መጣ» እያሉ ይሰማማሉ፡፡ የዚህን ጊዜ አርበኞች ወራሪውን አዘናግተው ጥቃት ይፈጽሙ ነበር፡፡ በዚህ አጋጣሚም የወደቀ መሣሪያ ያገኙ ነበር፡፡ አባት አርበኛ በጋሻውም «እኔም አጭር ምንሽር የሚባል መሣሪያ ይዤ ነበር» በማለት ያስታውሳሉ፡፡ በወረራው ወቅት ሴት፣ ወንድ፣ ትልቅ፣ ትንሽ ሳይባል በዱር በገደል ተሰዶ ነበር፡፡ በአባቶች የተገኘውን ይህን ነፃነት ወጣቱ ትውልድ የመጠበቅ አደራ እንዳለበትም ያሳስባሉ፡፡
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በዝግጅቱ ላይ እንደተናገሩት፣ ማህበሩ ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን ይህን የድል በዓል በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አካባቢዎች እያከበረ ነው፡፡ ከማህበሩ ጋር የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ፣ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲና የከተማው አስተዳደር፣ በጎንደርና በትግራይ ዓድዋ ላይ ይከበራል፡፡ ይህ የድል በዓል በእነዚህ አካባቢዎች በሚቀጥሉት ቀናትም እንደሚከበር ነው የተናገሩት፡፡
ይህ የድል በዓል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው የጥቁር ሕዝብ ድል እንደሆነ ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት፡፡ ኢትዮጵያን አርአያ በማድረግ በርካታ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ ወጥተዋል፡፡ ይህም አገሪቱ የነፃነት አገር እየተባለች እንድትጠራ አስችሏል፡፡
በበዓሉ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንትና የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር የበላይ ጠባቂ ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የሚያዝያ 27 የድል በዓል ኢትዮ ጵያውያን በነፃነታቸው ላይ እንደማይደራደሩ ለጠላትም ለወዳጅም ያሳየ ነው፡፡ ጣሊያን በዓድዋ ላይ የደረሰበትን ሽንፈት ለማካካስ ለ40 ዓመታት ያህል ተዘጋጅቶ ቢመጣም ዳግም ኪሳራ አጋጥሞታል፡፡ ይህ የኢትዮጵያ የአሸናፊነት ወኔ ለአገሪቱ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ላሉ ቅኝ ተገዥዎች የነፃነት ምሳሌ የሆነ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የነፃነት ተምሳሌት መሆኗን ለማወቅ የሩቁ እንኳን ቀርቶ በቅርብ ዓመታት ሰላም ላጡ አፍሪካውያን አገሮች አለኝታ መሆኗ ምስክር እንደሚሆንና በኩራት እንድንናገር ያደረገን ይኸው የአገሪቱ አንድነትና ነፃነት እንደሆነ ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት፡፡ የአገሪቱን ሰላምና ነፃነት ለማረጋገጥ የተደረገው ጥረት አሁን ላይ የአገሪቱ ጠላት በሆነው ድህነት ላይ እንዲደገም አሳስበዋል፡፡
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ጥር 1 ቀን 1931 ዓ.ም ተጉለት «አንቀላፊ» በተባለ ቦታ ላይ በአፍላው ጦርነት ወቅት የተቋቋመ ሲሆን የወቅቱ የበላይ ሰብሳቢ ስመ ጥሩ አርበኛ ራስ አበበ አረጋይ ነበሩ፡፡ 

 

ዜና ሐተታ
ዋለልኝ አየለ

 

 

 

Published in አጀንዳ

አዲስ አበባ፡- በተለያዩ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቤቶች ተማሪ የሆኑና በቴክኖቬሽን ኢትዮጵያ በተባለ ድርጅት ድጋፍ የተደረገላቸው ሴት ተማሪዎች 18 ዓይነት ችግር ፈቺ የሞባይል ሶፍትዌር መስራታቸውን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡ 

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ትናንት ሶፍትዌር የሰሩ ሴት ተማሪዎች የቅድመ ውድድር ማጣሪያ ፕሮግራም ላይ እንደገለጹት፤ በሴት ተማሪዎቹ ከተሰሩት ሶፍትዌሮች መካከል ለቅድመ ካንሰር ምርመራ፣ ለአካባቢ ጽዳት፣ መድኃኒቶች የት መድኃኒት ቤት እንደሚገኙ የሚያመላክት፣ ግብር ለመክፈል ተራ ለመያዝና ሌሎች አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተሰጥኦ ያላቸው ሴት ተማሪዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን ለማሳደግና በዘርፉ ተሰማርተው ሀብት የሚያመጩበትን አቅም ለመፍጠር እየሰራ መሆኑንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
ሚኒስትሩ በአሁኑ ወቅት በዓለም ሰፊ ሀብት እየፈጠሩ የሚገኙ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በመሆናቸው፣ ይህን ወደ ሀገሪቱ ለማምጣት በመጀመሪያና በሁለተኛ ደረጃ የሚገኙና ተሰጥኦው ያላቸው ሴት ተማሪዎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግርን ሊፈቱ የሚችሉ ሶፍትዌሮችን በመስራት ለገበያ እንዲያቀርቡ እገዛ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
መንግሥት ከሚመድበው የምርምር በጀት ውስጥ 20 በመቶው ለሴት ተመራማሪዎች እንዲውል መወሰኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ የንግድና የፋይናንስ ዘርፉን ይቀይረዋል ተብሎ በታመነበት የብሎክ ቼይን ቴክኖሎጂ ለማሰልጠን በተደረገው ጥረት የመጀመሪያ ሰልጣኞች ሴቶች እንዲሆኑ መደረጉን አመልክተዋል፡፡
በቴክኖሎጂ ዘርፍ ሴቶች ሶፍትዌር እንዲሰሩና ገበያ ላይ ወጥቶ ሀብት መፍጠር እንዲችል ሚኒስቴሩ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ጠቅሰው፣ በዓለም ደረጃ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ስመጥር በመሆን ሀብት ያፈሩት ቢልጌትስና ማርክ ዙከርበርግ በልጅነታቸው ክህሎቱን በማሳደግና ዓለምን የሚቀይር ሥራ በመስራታቸው መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
ሕፃናት ከልጅነታቸው ጀምሮ የቴክኖሎጂ ሀብት የሚያመነጩበት ዕድል መክፈት በሀገር ላይ ከፍተኛ የሆነ ሀብት የማመንጨት ሥራ በመሆኑ ዕድሉን መፍጠር እንደሚገባም ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች በሀገሪቱ ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያ ችግሮች ሊፈቱና ሥራን ሊያቃልሉ የሚችሉ የተለያዩ 18 ሶፍተዌሮችን መስራት የቻሉ ሴት ተማሪዎች በቴክኖቬሽን ኢትዮጵያ የተባለ ድርጅት ድጋፍ መደረጉን በፕሮግራሙ ላይ ተገልጿል፡፡

ዑመር እንድሪስ

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።