Items filtered by date: Monday, 07 May 2018

ከፊት «ኢትዮ» የሚል ቃል አስቀድመው «... የተሰኘው እውቅ የፖፕ የሙዚቃ ስልት አቀንቃኝ በ«ቢልቦርድ» የደረጃ ሰንጠረዥ አናት፣ ... «ሆሊውድ» ገባ፣ ተጫዋቹ በተወዳጁ ... ሊግ፣ አሰልጣኙ የ... ብሄራዊ ቡድንን ለታላቅ ስኬት አበቁ፣ ሼፉ በ... ቤተ-መንግስት ለፕሬዚዳንቱ ምግብ ያበስላል፣ ታዳጊዎቹ ... በተባለ የዘፈን ውድድር አሸነፉ፣ ...» የሚሉ ዜናዎችን መስማት ከጀመርን ዋል አደር ብለናል። የምስራቅ አፍሪካዊቷን የፍጥረታት መነሻ ሃገር፤ ከስሟ ሶስቱን ፊደላት ብቻ ተውሰው በሌላ ሃገር ስም የሚጠናቀቁ ዜግነቶች ያሏቸው ዝነኞችም በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን መግነናቸው እየተለመደ መጥቷል።
ሙሉ መሆን ፍጹማዊነትን ባይተካም በአንጻራ ዊነት ግን የብቁነት ማሳያ ይሆናል። የጎደለና ከቁጥር ያልሞላ ነገር በሁለት እግሩ ያልቆመ ነውና ሌላውን ሊወክልም አይችልም። እርግጥ ነው ግማሽ ከምንም ይሻል ይሆናል፤ ብቻውን ሊቆም ግን አይቻለውም። ለምሳሌ የሰው ግማሽ የለውም፤ አንድ ጎኑ እዚህ ሌላ ጎኑ ደግሞ እዚያ የሚባል ነገርም አይኖርም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ግማሽ ማንነት የበርካቶች ወሬ ማድመቂያና ማደናነቂያ የሆኑ ሰዎች መበራከታቸውን መታዘብ ይቻላል።
ለዚህ ትዝብት መነሻ የሆነኝም በየመገናኛ ብዙሃኑ የምንሰማቸውና በበርካታ ወጣቶች ዘንድ እንደ አርዓያ የሚታዩ እኛን የማይወክሉ ነገር ግን «የእኛ» የተባሉ ግማሽ ማንነቶች ናቸው። እርግጥ ነው እንደየሰዉ አስተሳሰብና ፍላጎት ተምሳሌት የሚሆኑ ሰዎችም የተለያዩ ናቸው፤ መብት መሆኑንም አከብራለሁ። ይሁን እንጂ «ዘር ከልጓም ይሳባል» የሚለውን ብሂል በራሳቸው መንገድ ተርጉመው አለመበጠሱ የሚያጠራጥረውን የሳሳ ክር ከራሳቸው ሊያገናኙ ሲሞክሩ ግራ ያጋቡኛል።
እነዚህ በዓለም ዝነኛ የሆኑ ግለሰቦች ውልደታ ቸውም ባይሆን እድገታቸው ከምዕራባዊያኑ ዘንድ ነውና በእነርሱው ዘይቤ የተቃኙ ናቸው። አንዳንዶቹማ ጆሯቸውን ቢቆርጧቸው እንኳ የትኛውንም ኢትዮጵያዊ ቋንቋ የማይሰሙ ናቸው። በርካቶቹ ደግሞ በኢትዮጵያ አለመኖራቸው ኢትዮጵያዊነታቸውን ያስረሳቸውና ትዝታም የሌላቸው ናቸው። ከዕውቅናቸው በፊትም ይሁን በኋላ ኢትዮጵያን ስለመጎብኘት ያላሰቡ፣ ቢጎበኟትም ከሌሎች ጉብኝቶች ያልተሻለ ቦታ እንዳልሰጧት ከመዘናጋታቸው መመልከትም ይቻላል። በአሜሪካና አውሮፓ ህዝብ የሚያጨበጭብላቸውና የሚያደንቃቸው እነዚህ ግለሰቦች፤ በስማቸው የሚጠራና ታሪካቸውን የሚያወሳ አንዲት እርምጃ አለመውሰዳቸውም ማንነታቸው ከእዚያ እንጂ ከእኛ አለመሆኑንም ነው የሚያሳየው።
በእኔ እሳቤ «ኢትዮጵያ»ን መተርጎም ከባድ ቢሆንም ስለ ኢትዮጵያዊነት መገለጫ ግን ብዙ ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያዊነት የአብሮነትና የጋራ ውጤት በመሆኑ፤ አየሯን ተንፍሶ፣ ውሃዋን ጠጥቶ፣ በምድሯ የሚኖር ብቻም ሳይሆን በደስታዋ ተደስቶ በሃዘኗም አለሁልሽ የሚላት ነው። በአንጻሩ «ላም አለኝ በሰማይ ወተቷን የማላይ» ይሉት ዓይነት ብሂል ባህር ማዶ ያለን ዝነኛ እየቆጠሩ «የእኛ» በሚል ኩራት መኮፈስ አይዋጥልኝም።
ከእነዚህ ይልቅ «የእናት ሆድ ዥንጉርጉር» ብለው ሃገራችንን ሃገራቸው አድርገው የሚኖሩና ለኢትዮጵያም በርካታ አስተዋጽኦዎችን የሚያበረክቱ የውጪ ዜጎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም። ታዲያ እነዚህ መልካም ሰዎች እያሉ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን በምናብ አሻግረው በማየት «ኢትዮጵ ያዊው፤ ኢትዮጵያዊቷ» በሚል ማንቆለጻጸስ ከተጀመረ ሰነባብቷል። እርግጥ ነው እናትም ሃገርም «ልጆቼ» ለማለት ጥቅምና እጅ መንሻ አያስፈልጋቸውም። ካሉበትና በየተሰማሩበት ልጅነታቸውን ማሳየት ቢገባቸውም፤ እኛ ግን በተቃራኒው «የእኛ» ናችሁ ማለት ከጀመርን ሰነባብተናል።
እነዚህ ግለሰቦች በሚሊዮኖች በሚቸበቸብ አልበማቸው፣ በሚያፍሱት ረብጣ ገንዘብና በምቾታቸው ልክ ማንነታቸውን ከእኛ አርቀዋል። አልፎ አልፎ ለስራቸው ማድመቂያ እንዲሆናቸውም በኮልታፋ አንደበታቸው የአማርኛ ቃላትንና ዜማዎችን ይቀላቅሉ ይሆናል። ነገር ግን ይህ ብቻውን ኢትዮጵያዊ አያሰኛቸውም፤ ምክንያቱም በዘር ያልተዋረሱን በርካቶች በስራዎቻቸው ላይ ኢትዮጵያን ገልጸዋታል። ለትዝብቴ ማብቂያ ይሆን ዘንድ አንድ ታሪክ ላውጋችሁ።
በሰፈራችን ከጠዋት እስከ ማታ ሲጭንና ሲያወርድ፣ ሲያጥብና ሲላላክ ይታያል። የትኛው ንም ስራም «አልችልም» ስለማይል፤ እገዛ የሚያስፈልገው ሲኖር በቅድሚያ ይጠራል። ለሰራበትም ቢሆን የሰጡትን ተቀብሎ አመስግኖ ከመሄድ ውጪ ፊቱ ሲጠቁር አይታይም። በዚህ ጸባዩም በሰፈሩ ነዋሪዎች ዘንድ ተወዳጅ በመሆኑ ከሚያገኛት ሽርፍራፊ ሳንቲም ላይ ትርፍ ጣል የሚያደርጉለት በርካቶች ናቸው።
ይኸው ባተሌ ከወላጆቹ በወረሰው ደሳሳ ጎጆ የሚኖር ሲሆን፤ ከረጅም ዓመታት በፊት ከሃገር የኮበለለ ወንድሙ ፎቶ ብቸኛ ቅርሱና መመኪያው ነው። ወንድሙ ከዓመታት በፊት አንዴ ወደሃገሩ ቢመጣም የወላጆቹን እርም አውጥቶ ብቻ ነበር ወደመጣበት የተመለሰው። ከዚያ በኋላ ወደዚያች ቤት ብቅ ብሎ ባያውቅም፤ ወንድሙ ግን «ባይሞላለት እንጂ አንድ ቀን መጥቶ ኑሮዬን ይደግፋል ያዘመመችውን የቤተሰቦቻችንን ጎጆም ያቃናል» እያለ ነበር በተስፋ የሚኖረው። ድንገት ታሞ ለአልጋ በተዳረገ ጊዜ ግን የደረሰለት ባህር ማዶ ያለ ወንድሙ ሳይሆን የቅርብ እሩቅ ያላቸው የሰፈሩ ሰዎች ነበሩ። ይኼኔ ታዲያ አጋጣሚው አስተምሮታልና «ከሩቅ ስጋ፣ የቅርብ ባዳ ይሻላል» ለማለት ተገደደ።
እናም ወገኖቼ ብዙ ሊባልልን ሲቻል፣ በብዙ ልንገለጽ ሲገባን፣ የበርካቶች መነሻና ተምሳሌት ሆነን ሳለ የሩቁን መናፈቅ ምን ሊባል ይችላል? ግማሽ ማንነትስ ዘርን ከልጓም ሊያስብ ይቻለዋል? እናስብበት መልዕክቴ ነው። ሰላም! ቸር እንሰንብት፡፡

 

የቆጡን አወርድ ብላ...

 

ከዚህ ቀደም የሰማሁትን አስገራሚ ዜና ላካፋላችሁ። ነገሩ እንዲህ ነው፤ አንድ ሌባ ሊሰርቅ ካቀደበት ቤት ሰው አለመኖሩን ያረጋግጥና ሰርስሮ ወደ ውስጥ ይዘልቃል። ገንዘብ የሚገኝበትን ቦታ በአይኑ እያማተረ በዚያውም ዋጋ የሚያወጡለትን ቁሳቁሶችም ይመራርጣል። እንዲህ እንዲህ እያለም ከመታጠቢያ ቤቱ ይደርሳል፤ ይሄኔ ታዲያ ለቅለቅ ብሎ እስኪመለስ ሰዎቹ እንደማይደርሱበት ገምቶ ወደ እጥበቱ ይገባል።
የአባወራውን ልብስ እንደራሱ መራርጦ ከለበሰ በኃላም የረሃብ ስሜት ይሰማዋል። ወደ ምግብ ማቀዝቀዣው በማምራትም ያገኘውን ይቀማምሳል፤ ሆድ ሲጠግብ ድካም ይከተላልና ጥቂት አረፍ ማለትም ያምረዋል። ሸለብ ካደረገው እንቅልፉ ሲነቃ ግን ራሱን ያገኘው በቤቱ ባለቤቶችና በፖሊሶች ተከቦ ነበር።
በየትኛውም መስክ ጥንቅቅ ያለ ስራን ማከናወን ከምስጋናም ባሻገር ሙያተኛ እንደሚያሰኝ ይታወቃል። አንዱን ስራ ሳይጨርሱ ያገኙትን ሁሉ መነካካት እና አቋራጭ መንገዶችን መፈለግም ሙያተኛ ወይም ጠንካራ ሰራተኛ ሊያሰኝ አይችልም። ምንም እንኳን ሌብነት እንደስራ የማይቆጠር እኩይ ምግባር ቢሆንም በጥንቃቄ አለማከናወን ግን ራስን ጉድጓድ እየቆፈሩ ከመሄድ የማይተናነስ ነው።
ታዲያ ከላይ ያሰፈርኩትን ታሪክ ለማውሳት ምክንያት የሆነኝ ከሰሞኑ የተሰማው ጉዳይ ነው። በፈረንጆቹ ስለመኖሩ ባላውቅም በእኛ ሃገር ግን ይህን መሳይ ጉዳይ ሲገጥም «የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች» ወይም «አተርፍ ባይ አጉዳይ» የሚሉ ተረትና ምሳሌዎችን ያስከትላል።
ጉዳዩ በእንግሊዝ የተከሰተ ሲሆን፤ ሌባው ለስርቆቱ ያመቸኛል ያለውን ሰዓት ጠብቆ ከአንድ መደብር ይገባል። ፊቱ በቀላሉ እንዳይለይም ስስ የእቃ መያዣ የፕላስቲክ ከረጢትን እንደ ጭምብል አጥልቆ ነበር ወደ ውስጥ የዘለቀው። ከአንደኛው መዓዘን ግን የደህንነት ካሜራ ይመለከታል፤ ካሜራውን ለማለፍ ዘየድኩ ያለው መላ ግን ራሱን ይበልጥ የሚያጋልጥ ነበር። ሌባው ካሜራዎቹ መልኩን ቀርጸው በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዳይውል በሸክላ አፈር ጭቃ ነበር የሸፈነው። ነገር ግን የደህንነት መሳሪያው የድረሱልኝ ጩኸቱን ወዲያውኑ በማሰማቱ ተደናግጦ መደብሩን ጥሎ እግሬ አውጪኝ ይላል።
በወቅቱ ፖሊሶች ከቦታው ሲደርሱም ወንጀለ ኛውን ሊደርሱበት አልቻሉም፤ ይሁን እንጂ በካሜራው ላይ ያገኙት ጭቃ ወደ ወንጀለኛው የሚያመራ ነበር። ለካንስ አጅሬ ወደ ስርቆቱ ሲገባ የእጅ ጓንት አላደረገ ኖሮ በጭቃው ላይ የጣት አሻራዎቹ ቁልጭ እንዳሉ ነበር። የሌስተር ከተማ ፖሊስም በዚሁ ታግዞ ወንጀለኛውን በህግ ሊያስቀጣ በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ማስታወቁን ዩፒአይ የተሰኘው ድረ-ገጽ ነው ያስነበበው።
የስርቆት ሙከራ የደረሰበት መደብር ተጎጂ ቢሆንም የሌባው አመጣጥ ግን አስገራሚ እንደነበረ ነው በድረ-ገጹ ያሰፈረው። የሌባው ድርጊት «ሆም አሎን» የተሰኘውን ፊልም የሚያስታውስ ሲሆን፤ የዓመቱ የ«ሰነፍ ሌባ» ሽልማት ቢኖር የሚገባው ለእርሱ ነው ሲሉም ተሳልቀውበታል።

ብርሃን ፈይሳ

Published in መዝናኛ

እግር ኳስ ደንብና ስርዓት አለው። ደንብና ስርዓቱን ለማስፈፀም የተደራጀ ተቋምና አመራርም አለው። ከአስተዳደሩ በተጓዳኝ በሜዳው ላይ ፍልሚያ የእያንዳንዱን ጨዋታ ደንብና ስርዓት የሚያስጠበቁ ዳኞችም እንዲሁ። ለስፖርቱ «የዓለም ቋንቋ» በሚል ለመሞካሸትና ተወዳጅነትንም ለማትረፍ ያስቻለውም በደንብና ስርዓት እንዲሁም በአስፈፃሚ አካላት መታጀቡ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል።

በርካታ ምዕተ ዓመታትን ባስቆጠረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ስፖርት ታሪክ፤ ዳኞች ለመጀመሪያ ጊዜ በፊፋ ተመዝግበው ታዋቂነትን ያገኙት በ1942 ዓ.ም መሆኑን «የኢትዮጵያ እግር ኳስ ጉዞ» በሚል በጋዜጠኛ ፈለቀ ደምሴ የተጻፈውና በ2005 ዓ.ም የታተመው መጽሃፍ ያወሳል። በጊዜው በኢንተርናሽናል ደረጃ የተመዘገቡት ኢትዮጵያዊያን አርቢትሮች ስድስት ሲሆኑ፤ ሌፍተናንት ኮሎኔል ገበየሁ ዱቤ፣ ጸጋዬ በቀለ፣ መንግስቱ በላይነህ፣ አየለ ተሰማ፣ መንገሻ ደብሩና መሃመድ ሰይድ መሆናቸውንም በመጽሃፉ ተቀምጧል።
ዓመታትን ተሻግሮም ይህ የዳኞቻችን ባህር አቋርጦ ጨዋታዎችን በብቃት የመምራት ተግባር ሲደበዝዝ አይስተዋልም። አሁንም በርካታ ኢትዮጵያዊያን ዳኞች የፊፋ ዕውቅና ስላላቸው በአህጉርና ዓለም ዓቀፍ ውድድሮች ላይ ጨዋታዎችን በመምራት ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ዳኞች ጨዋታን በመምራት ብቻም ሳይሆን ብቃት ባለው ተግባራቸው ሁሌም በምስጋና እና በአድናቆት የታጀበ ነው። ኢንተርናሽናል አልቢትር በአምላክ ተሰማንና ሊዲያ ተስፋዬን መጥቀስም ለዚህ በቂ ምስክር ይሆናል። እግር ኳስ በመዝናኛነቱ እንዲቀጥል ሰላማዊ የውድድር መድረክ መፈጠሩ የግድ ነው።
ይህ የዳኞች ዓለም አቀፍ ጨዋታን የመምራት ብቃት ግን በአገር ውስጥ ውድድሮች ሲፈተሽ መደብዘዝና በችግር መተብተብ ይስተዋልበታል። በዋነኛው ሊግ ኢትዮጵያ በፕሪሚየር ሊግ የሚያጫውቱ ዳኞችም የዚህ ሰለባ ሆነዋል። በተለይ ከደጋፊዎችና ከክለብ አመራሮች የሚደርሱባቸው ዛቻና ማስፈራሪያ ዘመናትን ተሻግሮ አሁንም ድረስ በየደረጃው በሚካሄዱ የሊግ ጨዋታዎች ላይ እየታየ ይገኛል።
ጨዋታዎች ከመካሄዳቸው አስቀድሞ በጨዋታዎቹ የመሸነፍ ስጋት የገባቸው የክለብ አመራሮች ዳኞችን በማስፈራራትና ሞራላቸውንም በመንካት ጨዋታዎችን እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ እንዲካሄድ ያደርጋሉ። በዳኛ ውሳኔ ምክንያት ለሽንፈት መዳረጋቸውን ያመኑ ደጋፊዎችና ውጤቱ ያልተዋጠላቸው ክለቦችና ተጫዋቾችም ውሳኔዎችን ማስቀየር ባይችሉም ዳኞች ላይ ማስፈራሪያ ማድረሳቸው የተለመደ ጉዳይ ሆኗል። በተለይ በዚህ ዓመት የተፈፀሙ ተደጋጋሚ ከዳኝነት ጋር የተያያዙ ውዝግቦች አለፍ ሲልም ድብደባዎች ዳኞች ላይ ያነጣጠሩ ናቸው። በዚህም ምክንያትም ዳኞች ለከፋ የአካልና የሞራል ጉዳት ተዳርገናል በሚል ከሳምንት በፊት ስራ እስከማቆም የደረሰ ውሳኔአቸውን አሳውቀዋል።
በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ዳኞች ሰው መሆናቸው እየተረሳና የሚሰጧቸው የተሳሳቱ ውሳኔዎችም ሰው በመሆናቸው የተፈጠሩ ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ ማለፍ እየቀረ መጥቷል። እያንዳንዱን የዳኛ ውሳኔ ከሙስናና ሌላኛውን ቡድን ከመጥቀም ጋር ማያያዝ በተመልካች፣ በተጫዋች፣ በአሰልጣኞች እንዲሁም በክለብ አመራሮች ዘንድ በእጅጉ ተለምዷል። በዚህም ምክንያት ውሳኔን በመቃወም ተጫዋቾች ዳኞችን ከበው ሲያዋክቡ ተመልክተናል።
በዳኝነት ውሳኔ ላይ የሚያጋጥመው ስህተት የጨዋታውን ውጤት ብቻም ሳይሆን ታሪክ ሊለውጥ የሚችል አቅም አለው። የእግር ኳሱ መንደር ፍልሚያን የመምራትና የውሳኔ አሰጣጥ ሁነት ደጋግሞ እንዳሳየን ዳኞች ሜዳ ውስጥ ስህተት አይሠሩም ማለት አይደለም። ዳኝነት በተለያዩ ምክንያቶች ሊዛባ ይቻላል፤ አንዳንዴ ግን በተለያዩ ምክንያቶች በተለይ ከህግ አተረጓጎም ጋር በተያያዘ በዳኞች በኩል ስህተቶች ሊፈጠሩና በበርካቶች ዘንድም ቅሬታዎች ሊያስተናግዱ ይችላሉ። እንዲያም ሆኖ ግን ዓለም ዓቀፉ የእግር ኳስ ህግ አውጪ አካል እንደሚስማማበት የዳኞች ውሳኔ 96 ከመቶ የሚሆነው ትክክል መሆኑን ነው።
ምንም እንኳን የዳኞች ስህተት የጎላ አይደለም ባይባልም፤ ሲከሰት ድርሻው ከፍተኛ ከመሆኑም ባሻገር ሌሎች ጉዳዮችንም ሊያስከትል ይችላል። በዚህ ምክንያትም ነው ፊፋ በዳኞች የሚከሰተውን የአራት በመቶ ስህተት ለመቀነስ በቪዲዮ የታገዘ ዳኝነትን ተግባራዊ ለማድረግ ከውሳኔ ላይ የደረሰው። ይህም ስህተቱን ሁለት በመቶ በመቀነስ ቀድሞ የነበረውን የዳኝነት ስህተት ሙሉ ለሙሉም ባይሆን እንደሚያስወግደው ታምኖበታል። በኢትዮጵያም በተለይ ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት በፕሪሚየር ሊጉ ለመሳሳት የሚከብዱ ስህተቶችን በመሥራት በደጋፊ ስሜት ላይ ቀዝቃዛ ውሃ የሚቸልሱና ለደጋፊዎች ስሜታዊነት መገንፈል ዋነኛ መንስኤ የሆኑ ዳኞች ተስተውለዋል።
ዳኞች በተለያዩ ጥቅሞች መደለላቸውም በአደባባይ መነገር ጀምሯል። በተለይ ሽንፈትን የደጋገሙና ውጤታቸውም ካሰቡት ደረጃ በታች ያደረጋቸው፣ ዋንጫ ለማንሳት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው፣ አንዳንዴም በወራጅ ቀጠናው ስጋት ውስጥ የገቡ ክለቦች ከዳኞች ጋር በመስማማት ህገወጥና ከሙያዊ ስነ-ምግባር ውጪ የሆነ ተግባር ውስጥ ይገባሉ። ጉዳዩ በየትኛውም ዓለም ያለ ተሞክሮ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚሰሙ ጉዳዮችም አሉ። በዚህ ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉት ዳኞች ጥቂት ቢሆኑም፤ ስማቸውን ለማጉደፍና ክብራቸውን ለመቀነስ ግን ምክንያት ይሆናሉ። በአንጻሩ የዳኛው የኋላ ታሪክ ከክለቦቹ ጋር ሊገናኝ ይችላል በሚል ጥርጣሬና ፍርሃት ብቻም ለእያንዳንዱ ክስተት ዳኞችን ተጠያቂ የሚያደርጉም በርካቶች ናቸው።
እዚህ ላይ መታወቅ ያለባቸው ሁለት አብይት ጉዳዮች አሉ። ቀዳሚው የግል ጥቅምና ፍላጎትን ታሳቢ በማድረግ ሆን ብሎ ውሳኔ የሚያዛቡ ዳኞች የመኖራቸውን ያህል፤ ጨዋታ በመምራት ብቃታቸው አንቱታን ያተረፉ መኖራቸውንም ነው። በዳኝነት ቅጽበታዊ የመሆኑ ስህተቶች መፈጠራቸው እሙን ሲሆን፤ ጨዋታውን ከሚመሩት ዳኞች መካከል ምናልባት አንደኛው የውሳኔ አሰጣጥ ችግር ፈጥሮም ይሆናል። ይህ ማለትም ሌሎቹ ዳኞች ስህተት ሰሪዎች ናቸው ማለት ግን አይደለም።
ለዚህ ምክንያት ከሚሆኑት ጉዳዮች መካከል አንዱ የዳኞች የብቃት ደረጃ አለመመጣጠን ነው። እንደየጊዜው ከሚሻሻሉ የስፖርቱ ህግጋት ጋር ራሳቸውን የማያራምዱና ጨዋታ በማንበብ ህጉን ወደ ተግባር በመለወጡ በኩል ችግር የሚስተዋልባቸውም ጥቂቶች አይደሉም። ይህ በጥቂት ስህተት ከፍተኛ ችግር ሊያደርስ የሚችል ሙያ በስልጠና መታገዙ የግድ ይሆናል። በነባራዊው ሁኔታ የሚታየውና በውይይት መድረኮቹ ላይ በዳኞች ከሚነሱ ጉዳዮች መካከልም ፌዴሬሽኑ በየዓመቱ በቂ የዳኝነት ስልጠናዎችን አለማዘጋጀቱ ነው። በፊፋና በካፍ ለስልጠናዎች በጀት የሚመደብ ቢሆንም ፌዴሬሽኑ ግን ትኩረቱን ከዚህ ይልቅ በሌሎች ስራዎች ላይ ማድረጉ በዳኛው ብቃት ልክ ውሳኔዎች እንዲወሰኑና ቅሬታዎች እንዲስተናገዱም ምክንያት ሆኗል።
በእግር ኳስ ዳኝነት ሙሉ በሙሉ ስህተት አይሠራም ባይባልም በዚህ ዓመት የእግር ኳስ ሊጎች ፍትሃዊ ያልሆነ የዳኝነት ውሳኔ በመስጠት የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት እንዳይፈጠርና የተሻለ ዳኝነት እንዲኖር በቂ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ጨዋታዎችን በብቃት የሚመሩና ለደጋፊዎች ስጋት የማይፈጥሩ ዳኞችን ለማፍራት ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል። የሊጉ ዳኞች የጤና ምርመራና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ፈተና እንዲወስዱና የተሻሻሉ የፊፋ ሕጎችን እንዲያውቁና ሕግን ባለማወቅ ፍትሃዊ ያልሆነ የዳኝነት ውሳኔ እንዳይሰጡ ማድረግም ይገባል። ከዳኞች በተጓዳኝ ተጫዋቾችና ተመልካቾች ስለ ተሻሻለው ሕግ በቂ ግንዛቤ ከሌላቸው ነገሩ ታጥቦ ጭቃ እንደመሆኑም ለሁሉም የስፖርት ተዋናዮች ከወዲሁ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል።
ደጋፊዎችን ለፀብ የሚጋብዙ የዳኝነት ውሳኔዎች ለመቀነስ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በዳኞች ብቃት ላይ ጠንክሮ መሥራት ይኖርበታል። ለዳኞች ተከታታይ ስልጠናዎች በመስጠት ጨዋታንና የደጋፊ ተጽዕኖን የሚቆጣጠሩበት ጥበብ ሊያስተምራቸውም ይገባል። ከዳኞች በተጨማሪም ደጋፊን የሚያነሳሱ ሥርዓት አልበኛ ተጫዋቾችን የሚገራና ከውሳኔ በኋላ ዳኛን የማዋከብ ድርጊቶችን ለመከላካል የሚያግዝ ደንብ ማውጣትም የግድ ይለዋል። ደህንነት ተሰምቷቸው ስራቸው ላይ እንዲያተኩሩም የሚገባቸውን ማሟላት እንዲሁም አቅምና ብቃታቸውን መገምገምም ያስፈልጋል። በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ፌዴሬሽኑ ዛሬ ነገ ሳይል የቤት ስራውን ማከናወን ይኖርበታል፡፡ ዳኞችም ራሳቸውን ለማጎልበት መጣር ይጠበቅባቸዋል።

ብርሃን ፈይሳ

 

Published in ስፖርት

“እውቀት የሁሉ ነገር መሠረት ነው” የሚል ብሂቅ ቅቡል ቢሆንም፤ እውቀት እንዴትና ከየት ይገኛል? እንዴትስ ይለካል? የሚሉ ጉዳዮች ግን የተለያየ ሀሳብ ሊሰነዘርባቸው ይችላል፡፡ በዓለማችን ተጨባጭ ሁኔታም የእውቀት መቅሰሚያ ተደርገው የሚወሰዱት ትምህርት ቤቶች ሲሆኑ፤ ተማሪዎች ፊደል ከመቁጠር በዘለለ የምርምር ሥራዎችን እስከማፍለቅ የሚያስችሉ ሂደቶችን የሚያልፉበት መድረክም ነው፡፡
ተማሪዎች ይማራሉ፣ ያውቃሉ፣ ያወቁት ይመዘንና ብቁ ሆነው ሲገኙ ወደቀጣዩ የትምህርት ደረጃ ይሸጋገራሉ፡፡ በሂደቱም ተማሪዎች በፈተና መውደቅን ስለማይፈልጉ ውጤታማ ለመሆን፣ ከሌሎች ልቆ ለመገኘት፣ አዳዲስ እውቀቶችን ለመቅሰም፣ ሩቅ ሆኖ የሚያዩትን በቅርብ ለመዳሰስ እንዲነሳሱና ለዚሁም እንዲተጉ ያደርጋቸዋል፡፡ ከዚህ በተቃራኒም አሁን አሁን የፈተና ኩረጃ እየተበራከተ በመምጣቱ ተማሪዎች አውቀው ሳይሆን በሌሎች ላይ ተንጠልጥለው እንዲጓዙ፣ በራስ ሳይተማመኑና በራስ መቆም ሳይችሉ የሌሎች ጥገኛ እየሆኑም ይገኛል፡፡
ለዚህ አብይ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ በተለይ የ10ኛ እና 12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናዎች ናቸው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እነዚህን ፈተናዎች ለማለፍ ሲባል የተለያዩ የኩረጃ ስልቶች እየጎለበቱ መጥተዋል፡፡ ለዚህ ተግባር ደግሞ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ቤተሰብ፣ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም የፈተና ግብረ ሃይል አባላት ሳይቀሩ የኩረጃ ሂደቱ ተባባሪ ሲሆኑ ይታያል፡፡ የአገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲም ይህን ችግር ለመፍታት የፈተናዎች ማስፈጸሚያ የንቅናቄ ሰነድ አዘጋጅቶ ሰሞኑን ከባለድርሻዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ እኛም ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ የዚህን ሰነድና ውይይት ፍሬ ሀሳብ ለንባብ በሚመች መልኩ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
መነሻ
በ2010 የትምህርት ዘመን የሚሰጡ አገራዊና ክልላዊ ፈተናዎች ደህንነታቸው የተጠበቀና የሚፈለገው ውጤት እንዲመዘገብባቸው በከፍተኛ ጥንቃቄና ስነምግባር ሊመሩ ይገባል፡፡ ይሄም በፈተና ህትመት፣ ስርጭትና አስተዳደር ብቃት ያላቸው የፈተና አስፈጻሚዎችና ደጋፊ ባለሙያዎችን በማሰማራት ተገቢውን የፈተና አስተዳደር በጀት በመመደብ፣ የተቀናጀና የተናበበ የአህዝቦት ሥራ በመስራት ተፈታኞችን ሊያጋጥሙ የሚችሉ የተለያዩ ውዥንብሮችን በማስወገድ በተረጋጋ ሥነልቡና እንዲፈተኑ ማድረግ ደግሞ የምርጫ ጉዳይ አይደለም፡፡
በመሆኑም ሁሉን አቀፍ አገራዊ ንቅናቄ በመፍጠር በ2008 ዓ.ም እና ከዚያ በፊት ይከሰቱ የነበሩትን ከፈተና ዝግጅት፣ ህትመት፣ ስርጭትና ከፈተና አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ዳግም ሳይከሰቱ ሠላማዊና በተረጋጋ ሁኔታ መምራት አስፈላጊ ነው፡፡ የንቅናቄ ሰነዱም ለዚሁ የሚያግዝ ሲሆን፤ ለተጠቀሱት ተግባራት በብቃት መከናወንና ውጤታማነት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና በባለቤትነት ስሜት መስራት ወሳኝ ነው፡፡
የተከናወኑና እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት
ለፈተናዎቹ መሳካት የሚያስችሉ ከህትመት እስከ ስርጭት ያሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ መካከልም የተፈታኞች ምዝገባና የመረጃ ማጣራት ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ለአንድ ሚሊዮን 200 ሺ 767 የ10ኛ እና ለ284ሺ 312 የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች የፈተና አዳራሽ መግቢያ ካርድ (አድሚሽን ካርድ) ህትመት እየተከናወነ ይገኛል፡፡ እስከ ሚያዝያ 30ቀን 2010ዓ ም ይሰራጫል፡፡
ፈተናዎችም ተገቢነታቸው፣ አስተማማኝነታቸ ውና ፍትሃዊነታቸውን ጠብቀው እንዲዘጋጁ የተደረገ ሲሆን፤ የአሥረኛ ክፍል ሙሉ ለሙሉ፣ የ12ኛ ክፍል ደግሞ 95 በመቶ የሚሆነው የህትመት ሥራው ተጠናቅቋል፡፡ በዚህም ለ10ኛ ክፍል 29፣ ለ12ኛ ደግሞ 11፣ በድምሩ 40 የትምህርት አይነቶችን በማሳተምና በማደራጀት በ139 የጉዞ መስመሮች ለማሰራጨት ቅድመ ዝግጅት ተጠናቅቋል፡፡
የስርጭት ጉዞውም በሚወጣው መርሐ ግብር መሰረት ከየክልሉ በሚመረጡ ጠንካራና ታማኝ የትምህርት ባለሙያዎችና በተመረጡ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ታጅቦ በየብስና አየር ትራንስፖርት የሚከናወን ሲሆን፤ በተመሳሳይ ከዋና መውረጃ ወደ ትምህርት ቤቶች ወይም ፈተና ጣቢያዎች የሚደረግ የስርጭት ቅብብሎሽም በጥብቅ ዲስፕሊን ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል፡፡ ፈተናዎችም ከቦታ ቦታ የሚጓጓዙት ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ብቻ ይሆናል፡፡ እስከ ፈተናው ዕለትም ሙሉ ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡
የቀደሙ ልምዶችና የአሁን ስጋት
አንድ ተማሪ በተማረበት ሙያ ራሱንም ሆነ አገሩን ሊጠቅም የሚችለው ሙያውን በአግባቡ ሲያውቅና የሚሰራበትን አቅም መፍጠር ሲችል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ተማሪዎች ፈተናን ለማለፍ ብቻ ሳይሆን የተሻለ እውቀትን ለማገኘት መማር፣ ማጥናትና መፈተን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ አኳያ ቀደም ባሉት የፈተና ጊዜያት ተማሪዎች በብጫቂ ወረቀት ጽፎ ከመግባት፣ ሊፈተሹ በማይችሉ የሰውነት አካላት ላይ ጭምር በመጻፍ ፈተናን ለመስራት ሲጥሩ ታይተዋል፡፡ ቴክኖሎጂንም ለፈተና ኩረጃ ተግባር እስከመገልገልም ተደርሷል፡፡ ይህ ሆኖም ውጤቱ በሚፈለገው ልክ ሳይሆንላቸው፤ በራስ መተማመናቸውንም አሳጥቷቸው አልፏል፡፡ አሁንም በዚህ አይነት አስተሳሰብ ውስጥ ያሉ ተማሪዎች አይኖሩም ማለት አይቻልም፡፡
በተመሳሳይ የተማሪዎችን ውጤታማነት የሚናፍቁ ቤተሰቦችና አካላት የመኖራቸውን ያክል ለፖለቲካ ጥቅማቸው ሲሉ የተለያዩ ውዥንብሮችን የሚያሰራጩ አካላት ቀደም ሲል ታይተዋል፡፡ ተማሪዎችና ቤተሰቦችም የነዚህ አካላት መጠቀሚያ በመሆን፤ ለልጆቻቸው የሀሰት መልስ እስከመግዛት ሲደርሱ ታይቷል፡፡ ይህ ደግሞ ቤተሰብን ላልተገባ ወጪ፣ ተማሪዎችንም ላላስፈላጊ ጭንቀት የሚዳርግ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ አሁንም ቢሆን እነዚህ ኃይሎች የማህበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም ከዚህ የሀሰት ማወናበጃ ተግባራቸው አልታቀቡም፡፡
ለፈተናው የሚመደቡ የፈተና አካላት (ፈታኞች፣ ሱፐርቫይዘሮች፣ የፈተና ጣቢያ ኃላፊዎችና የጸጥታ አካላት) እንዲሁም መምህራን በአንዳንድ አከባቢዎች የኩረጃ ተባባሪ ሲሆኑ፤ የፈተና ወረቀቶችን በስርቆት አውጥቶ በመምህራን ከማሰራትና ተማሪዎችም እርስ በእርስ እንዲኮራረጁ እስከመፍቀድ የሚስተዋል ተግባር ተስተውሏል፡፡ ፈተና ከውጭ ተሰርቶ ወደ ውስጥ የመግባቱ ሂደት እየተለመደ ሄዷል፡፡ ይሄም እንደ ትልቅ ልምድ ወደ ስምንተኛ ክፍል እየተዛመተ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የፈተና ሥነምግባር መመሪያን መተላለፍ ብቻ ሳይሆን ተማሪዎች ይሄንኑ ተስፋ እንዲያደርጉና ራሳቸውን ችለው እንዳይቆሙ በማድረግ በተማሪዎች ህይወት ላይ መቀለድ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ይህ አስተሳሰብ ነጥፏል ማለት አይቻልም፡፡
ከዚህ ባለፈ ግን ባለፈው የፈተና ሂደት ክፍተት ይታይባቸው የነበሩ ከመጓጓዣ፣ ከፈተና ደንብ ጥሰት፣ የፈተና አካላትን ከመመልመልና መመደብ፣ የተናበበ የመረጃ ልውውጥ መዘርጋትና መሰል ጉዳዮች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ የፈተና ደንብ ጥሰት ሲከሰት በቂ ባይሆንም በተማሪዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ግን ለዚህ ምክንያት የሚሆኑ የፈታኞች፣ የሱፐርቫይዘሮችና የጣቢያ ኃላፊዎች ሲቀጡ አለመታየት ሊታረም የሚገባው ስጋት ነው፡፡
የመፍትሄ ሀሳቦችና እርምጃዎች
በፈተና እሸጋ፣ በጭነትና ስርጭት ሂደት የሚስተዋሉ ችግሮች ካለፈው ሂደት ልምድ በመወሰዱ ዘንድሮ በአግባቡ እየተከናወነ ሲሆን፤ በ24 ሰዓት የካሜራ ቁጥጥር ስር ሆነው እየተሠራ ነው፡፡ ከጭነት ወረፋ ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ለመፍታትም ሁለት መጋዘን ተዘጋጅቶ በአንድ ጊዜ እስከ አራት መኪና መጫን የሚያስችል ሁኔታም ተመቻችቷል፡፡ የመረጃ ልውውጥ ሂደቱን የተሳለጠና የተናበበ ለማድረግ በኤጀንሲ ደረጃ ንዑሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረዋል፡፡ ክልሎችም በዚህ መልኩ አዋቅረው መስራትና ለሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢውን ፈጣን ምላሽ የሚያስገኝ አሰራር መዘርጋት አለበት፡፡
ወላጆችም ልጆቻቸውን ማገዝ የሚገባቸው የተሳሳተ መልስ በመግዛት ሳይሆን በአግባቡ እንዲያጠኑ በማድረግ መሆን አለበት፡፡ የፈተና አባላት ምልመላና ምደባ ሲካሄድ በተቀመጠው መስፈርት መሆን አለበት፡፡ በተማሪዎች የሚታየውን የዲስፕሊን እርምጃ አይነት እርምጃ በፈታኞችና ሱፐርቫይዘሮች ላይ መወሰድ ይገባዋል፡፡ ይሄንን ማድረግ ደግሞ በየአካባቢው ያለ የትምህርት አካል በተለይም የትምህርት ቢሮዎችና ለዚህ የተቋቋመው ግብረ ሃይል ነው፡፡
ከፈተናው ሂደት ጋር በተያያዘ በየዓመቱም አዳዲስ ችግሮች የሚስተዋሉ እንደመሆኑም ይሄን መሰረት ያደረገ ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀትም ያስፈልጋል፡፡ ሊያስጨንቅ የሚገባው መጨረሻ ላይ የሚገኘው ውጤት መሆን ስላለበትም ማንኛውም ባለድርሻ ከይዘት፣ ከጸጥታ፣ ከአስተዳደር፣ ወዘተ አኳያ ምላሽ የሚሰጡ ስድስት ያህል አገራቀፍ ንዑሳን ኮሚቴዎች ተቋቁመው ወደሥራ እንዲገቡ ከውሳኔ ተደርሷል፡፡
መልዕክት
የመፈተኛ አካባቢን ምቹ ማድረግ ከቤተሰብ ጀምሮ ህብረተሰብ፣ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች በየደረጃው ያሉ የሁሉም አካላት ድርሻ ነው፡፡ ሁሉም አካል ሥራውን በኃላፊነት ማከናወን በእነዚህ ተማሪዎች ህይወት ላይ የመወሰን ጉዳይ ነው፡፡ መልካም ሲሰራ ውጤቱ ያምራል፤ መልካም ትውልድም ማፍራት ይቻላል፡፡ አሰራሩ ከተበላሸ ግን ውጤቱም የተማሪዎቹም ህይወት ይበላሻል፡፡ በመሆኑም ከቤተሰብ ጀምሮ ሁሉም ባለድርሻ ይሄንኑ አውቆ መስራት ይጠበቃበታል፡፡
ተማሪዎችም ለተለያዩ አሉባልታዎች ራሳቸውን ሳያጋልጡ ባላቸው ጊዜ በእውቀትም በስነልቦናም በመዘጋጀት ተረጋግተው መፈተን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ወላጆችና ትምህርት ቤቶችም ባለው ጊዜ ውስጥ ተማሪዎችን መደገፍ፣ በስነ ልቦና ማዘጋጀት፤ ምቹ የፈተና ድባብ መፍጠርም ያስፈልጋል፡፡
በተለያየ መልኩ የሚነዙ ውዥንብሮችም አሳሳችና አደናጋሪ እንጂ ትክክለኛነት የሌላቸው መሆኑም ለማስረዳትም የህዝብ ግንኙነት ሥራውን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆን ተማሪው ለውዥምብሮች ቦታ ሳይሰጥ ተረጋግቶ ይፈተናል፤ ወላጆችም የፈተና መልስ በሚል የተሳሳተ መረጃ ከመሸመት ይቆጠባሉ፤ ፈተና የማይፈራና በራሱ የሚተማመን ተማሪ መፍጠርም የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት ይቻላል፡፡

ወንደሰን ሽመልስ

Published in ማህበራዊ

በአንድ አገር በሚኖር የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስርዓት ውስጥ መንግስትና ህዝብ ሊወጡ የሚገባቸው የየራሳቸው ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ይህ የመብትና ግዴታ መርህ ሲሆን፤ በሥርዓቱ ውስጥ የመልካም አስተዳደር መስፈንና አለመስፈንም በዚሁ የመብትና ግዴታ ትስስር እውን መሆን ውስጥ ሊታይ ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታም ይህ የመልካም አስተዳደርና ኪራይ ሰብሳቢነት ጉዳይ በበርካታ ችግሮች የተተበተበና ይበልጡኑ በኪራይ ሰብሳቢነት ታጅቦ ምህዳሩን በማስፋቱ ችግሩ ከመጠን ባለፈ ሁኔታ ስር እየሰደደ ይገኛል፡፡

አቶ ተሻለ ሰብሮ


በመንግስት ተቋማት ስር የሰደደው ይህ በሽታ በህብረተሰቡ ላይ ጫና በማሳደሩ፣ ህዝቡ የዚህን መጥፎ ምግባር ጠረን ለማስወገድ በእጅጉ ታግሏል፤ ለጥልቅ ተሃድሶ መሰረትም ሆኗል፡፡ ዛሬም በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አንደበት የመልካም አስተዳደር ችግርና የኪራይ ሰብሳቢነት ጉዳይ በቀይ መስመር ማዕቀፍ ውስጥ መግባታቸው ታውቆ ሊሰራ እንደሚገባ ተነግሯል፡፡ ለመሆኑ የመልካም አስተዳደር ባህርይና መገለጫ፣ አሁን በአገሪቱ የደረሰበት ደረጃ እና እየተወሰደ ካለው እርምጃ አኳያ፣ ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀይ መስመር ውጤት ያመጣ ይሆን? እንዴት ቢሰራስ ችግሩን ማቃለል ይቻላል? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን አነጋግረን እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል፡፡


መልካም አስተዳደርና ኪራይ ሰብሳቢነት


አቶ ተሻለ ሰብሮ፣ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ ምንም እንኳን ኪራይ ሰብሳቢነት ወይም ሙስና ብሎም መልካም አስተዳደር የሚሉ ጽንሰ ሀሳቦች ሳይንሳዊና ጥናታዊ ትርጓሜ የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም፤ በኢትዮጵያ መንግስት አስተዳደራዊና ርዕዮተ ዓለማዊ ተጨባጭ ሁኔታ እንዲሁም ከህገመንግስቱ አንጻር መመልከት ይቻላል፡፡ ከዚህ አኳያ የመልካም አስተዳደር ችግር ከህገ መንግስቱ ባፈነገጠ መልኩ ህዝብን ማገልገል ሲሆን፤ ኪራይ ሰብሳቢነት ደግሞ ከመልካም አስተዳደር ችግር የሚመነጭ ከህገ መንግስቱ አሰራር ውጪ ህዝብን እየበደሉ ለራስ ጥቅም መቆም ነው፡፡ በጥቅሉ እነዚህ ሁለት ጉዳዮች ህገ መንግስቱን ከመተግበርና አለመተግበር ጋር ተቃኝተው የሚታዩና የሚገለጹ ናቸው፡፡


የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ጉዑሽ ገብረስላሴም በዚህ ሀሳብ ይስማማሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ የመልካም አስተዳደርና ኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች አብዛኞቹ በባህሪያቸው አሰራሮችን ለህዝብ ሳይሆን ለግል ጥቅም ማዋል ላይ ተመርኩዘው የሚገለጹ ሲሆን፤ ይሄም የህዝብና የአገርን ጉዳይ በመርሳት ወደ ግል ኑሮ በማዘንበል በሚሰሩ የሽርክናና የጥቅም ኔት ወርክ ተሳስሮ የአገሪቱንና የህዝቡን ሀብት ማባከን ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሁለቱም ተነጣጥለው የሚታዩ አይደሉም፡፡


እነዚህኑ ሀሳቦች የሚያጠናክሩት ደግሞ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲና ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ መልካም አስተዳደር ጠፋ የሚባለው ባጠቃላይ ህዝብን ለማገልገል የተቋቋሙ ተቋማት ህዝብን ማገልገል አቁመው ለግላቸው ጥቅም ሲንቀሳቀሱ፣ ፍትህ ሲጠፋ፣ አስተዳደር ሲበላሽ፣ ሙስና ሲሰፋና መሰል ጉዳዮች ሲታዩ ነው፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነትም ከዚሁ የሚመነጭ ሲሆን፤ ይሄም ያልሰሩበትን ጥቅም የማግኘት አካሄድ ነው፡፡ አንድ አካል ወይም ቡድን ሳይሰራ አግባብ ባልሆነ መንገድ የመንግስት ተቋማትን በመጠቀም የህዝብ ሀብትን እየዘረፉ ለራስ ሀብት ማካበት፤ ማለት ነው፡፡
የችግሩ ምክንያቶች
እንደ ዶክተር መረራ ገለጻ፤ የመልካም አስተዳደር ችግርም ሆነ ኪራይ ሰብሳቢነት መከሰት ዋናው ምክንያት እና ጉዳይ ተጠያቂነት ያለው መንግስት ማቋቋም አለመቻል ነው፡፡ ተጠያቂነት ያለው መንግስት የሚመጣው ደግሞ በህዝብ ምርጫ ነው፡፡ ይህም ህዝብ በነጻነት መምረጥ ሲችል፤ ችግር ሲፈጥርም ማውረድ ሲችል ነው፡፡ ይህ መሆን ሳይችል ግን የመልካም አስተዳደር ችግር ይገዝፋል፤ ኪራይ ሰብሳቢነትም ይንሰራፋል፡፡
አቶ ጉዑሽ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ መንግስት የሚመረጠው በህዝብ ነው፤ ህዝቡ ደግሞ እንዲሰራለት ነው የሚመርጠው፡፡ ይወክለኛል፣ ይመራኛል፣ ይሰራልኛል፣ ችግሬንም ይፈታልኛል ብሎ ነው የሚመርጠው፡፡ ይህ የመምራትና የመስራት ኃላፊነት መከናወን ያለበት ደግሞ በአገሪቱ ህግ መሰረት ነው፡፡ በመሆኑም ህዝብ የመረጠው ኃላፊ በሕገ መንግስቱ መሰረት ህዝቡን በአግባቡ ካላገለገለው የመልካም አስተዳደር ችግር ይፈጠራል፡፡ በመሆኑም የመልካም አስተዳደርም ሆነ ኪራይ ሰብሳቢነት የመንግስት አካላት የተሰጣቸውን ኃላፊነት ዘንግተውና በጥቅም ጥላ ስር በኔትወርክ ተሰባስበው የጥቀመኝ ልጥቀምህ መስመር ውስጥ የመግባታቸው ውጤቶች ናቸው፡፡
በዚህ መልኩ ያሉ ኪራይ ሰብሳቢዎችም የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመዘንጋት ለግል ጥቅማቸው ሲሰሩ፣ ህዝብን ማገልገል ሲገባቸው ህዝብን ማገልገል ካልቻሉ፣ የአገሪቱን አጠቃላይ የፖለቲካ ሁኔታ ያዛባሉ፤ በልማት ሂደቱ ውስጥም የፋይናንስ አቅም እንዲዳከምና ስራ አጥነት እንዲበዛ ያደርጋሉ፡፡ ፍትህ ይዛባና በላድርግልህ አድርግልኝ የተተበተበ ይሆናል፡፡ አሁን በአገሪቱ እየታየ ያለውም ይሄው ስለሆነም፤ እነዚህ የመልካም አስተዳደርና ኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች ካልተፈቱ የህዝቡን ኃላፊነት መወጣት አይቻልም፡፡


ችግሩ ያለበት ሁኔታ


ህብረተሰቡ ኑሮውን ለመምራት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አገልግሎቶችን እንደሚጠይቅ የሚናገሩት አቶ ጉዑሽ፤ በአንጻሩ ከቀበሌ ጀምሮ ወደላይ ባሉት መዋቅሮች አጠቃላይ የህዝብን ስራ መስራት አለመቻላቸውን ይገልጻሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታም የህዝቡን ሀብት እያባከኑ ለራስ ጥቅም ከማዋል ባለፈ የህዝቡን አቤቱታ እየሰሙ አለመሆናቸውን፤ አገልግሎት ላለመስጠትም ቢሮ ዘግተው ተቀምጠው ህዝቡን እያስለቀሱ እንደሚገኙም ይገልጻሉ፡፡

አቶ ጉዑሽ ገብረሥላሴ


እንደ አቶ ጉዑሽ ገለጻ፤ እነዚህ አካላት የህዝብን ስራ መስራት እስካልቻሉ ድረስ የሚጠይቃቸው አካል ካለ ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ እነዚህን አካላት የሚጠይቃቸው ህዝብ ነው፤ ነገር ግን ለዚህ ህዝብ መድረክ አመቻችቶ የሚሰጠው የመንግስት መዋቅር ስለሌለ ህዝቡ እያለቀሰ ዝም ብሎ ተመልካች ሆኖ ቆይቷል፡፡ እነዚህ የመንግስት አካላት ደግሞ ህዝቡን እስካላገለገሉና እስካላስደሰቱ ድረስ ተጠያቂ መሆን አለባቸው፡፡
ዶክተር መረራ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ አሁን በአገሪቱ ያለው የኪራይ ሰብሳቢነትም ሆነ ሙስና ከፍተኛውና የመጨረሻው ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ ለዚህም ነው ህዝቡ በተለይም ወጣቱ ባመነበት መልኩ ችግሩን ለማቃለል ባደረገው እንቅስቃሴ በመላው አገሪቱ ችግሮች እየተፈጠሩ ያሉት፡፡ የዚህ ሰፊ ተቃውሞ ምንጩም ይሄው የመልካም አስተዳደርና ኪራይ ሰብሳቢነት መግዘፍ ነው፡፡ ለአብነት፣ ገሃድ ከወጡ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራት አንዱ የመሬት ዘረፋ ሲሆን፤ የመንግስት አካላት በመሬት ንግድ ላይ መሰማራታቸው ለግጭቱ መቀስቀስ ምክንያት ሆኗል፡፡ ከመልካም አስተዳደር መጥፋት አኳያም ሲታይ የፍትህ መጓደልና መጥፋት አንዱ ሲሆን፤ በአንድ አገር ገለልተኛ ዳኝነት ከሌለ ደግሞ የሚፈጠረው ይሄው ችግር ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ በሁለቱም መንገድ የመንግስት ተቋማት ተበላሽተዋል፡፡ እንደ አቶ ተሻለ ገለጻ ደግሞ፤ የመልካም አስተዳደርና ኪራይ ሰብሳቢነት ጉዳዮች ኢህአዴግ ገና በእንጭጩ እያለ የተስተዋሉ ሲሆን፤ ጥርስ ማብቀል ሲጀምር እንደመቅጨት ዛሬ ላይ ሰላሳ ሁለት ጥርሶች እንዲያበቅሉና በሁሉም እንዲነክሱ ተደርጓል፡፡ ይህም ባለማወቅ የተደረገ ሳይሆን ሆን ተብሎ የተደረገ እንደመሆኑ ሕግን መተላለፍና ሕገ መንግስት መጨፍለቅ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሊጠየቅ የሚገባው ግለሰብ ብቻ አይደለም፡፡ ከግለሰብ ባለፈ ስርዓቱ ነው መከሰስና መጠየቅ ያለበት፡፡
ምክንያቱም ህዝብን እየነከሱና እያስለቀሱ ያሉ ግለሰቦች ብቻ አይደሉም፤ ስርዓቱ የፈጠራቸው የሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈጻሚ አካላትም እንጂ፡፡ እነዚህ አካላት ችግሩ እንዲታረምና ሙስና መንግሥታዊ ተግባር ሆኖ የሚወሰድበት ደረጃ እስኪደርስ ለማረቅ ባለመስራ ታቸው የመልካም አስተዳደርም ሆነ ኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች አካል ናቸው፡፡ በመሆኑም በዚህ ደረጃ ሕገ መንግሥቱ እስኪጣስ ዝም ያለው መንግሥት እንደመሆኑ መጠየቅ ካለበትም የስርዓቱ ባለቤት መንግሥት ነው፡፡


የተጠያቂነት ሁኔታ


አቶ ተሻለ እንደሚናገሩት፤ በየጊዜው እንደሚሰማውና ከፌዴራል የኦዲት መስሪያ ቤት እንደሚነገረው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ትላልቅ ፕሮጀክቶችና የመንግሥት የልማት ተቋማት ሳይቀሩ የሕዝብ ሀብትን እያባከኑ ነው፡፡ በእነዚህ አካላት ላይ ግን እርምጃ ሲወሰድ አልታየም፡፡ ይህ ደግሞ ተጠያቂም፣ አስጠያቂም፣ እርምጃ ወሳጅም አለመኖሩን አመላካች ነው፡፡ ሆኖም ችግሩ በአንድ ግለሰብ ፋይል ከፍቶና አስፈርዶ የሚቆም አይደለም፡፡ እንደ ሥርዓት ነው ምላሽ ማግኘት ያለበት፡፡ ሆኖም ሕዝብ እንዳይቀጣው የዴሞክራሲ ስርዓቱ አመቺ አይደለም፤ መንግሥት ደግሞ ችግሩን እንዳይፈታ ራሱ ከሳሽ፣ ራሱ ተከሳሽ፣ ራሱም ፈራጅ ሆኖ መቅረቡ ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ነው እስካሁን ባለው ሂደት ደፍሮ ችግሩን ለመፍታት ያልተንቀሳቀስውና ትላልቆቹን ትቶ ትናንሾቹ ላይ ያተኮረው፡፡

ዶክተር መረራ ጉዲና


አቶ ጉዑሽ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ችግሩ በዚህ መልኩ መግዘፍ የቻለው የጥቅም ጉዳይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እነዚህ የመንግሥት ኃላፊዎችና ሰራተኞች ህዝቡን አላገለግል ሲሉና ኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር ውስጥ ሲዘፈቁ ኃላፊነት የተሰጠውና ሕዝብ የመረጠው መንግሥት እርምጃ አልወስድ ስላለ ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤትና ሌሎችን የሕግ አካላት ችግሩን ከመከላከል ይልቅ ሕዝብ ሲዘረፍና ሲያለቅስ፤ ለጉዳዩም ፈጻሚና አስፈጻሚ አጥቶ ሲንገላታ ዝም ብለው ነው ተመልካች የሆኑት፡፡ በዚህ መልኩ የሕዝቡ ምሬት መብዛትና ለችግሩም ምላሽ ሰጪ መጥፋት ነው ለአገሪቱ ሰላም መደፍረስ ምክንያት የሆነው፡፡
ዶክተር መረራም ይሄንኑ ሀሳብ ያጠናክራሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ ምንም እንኳን ችግሩ የገነነ ቢሆንም በችግሩ ልክ በአጥፊዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ አይደለም፡፡ ትናንሾቹን ከመልቀም ባለፈ ወደ ትላልቆቹ ደርሶ የእርምት እርምጃ መውሰድ አልተቻለም፡፡ ለችግሩ እየተበራከተ መምጣትም አንዱ ምክንያት ይሄው ሲሆን፤ በተለይ በትላልቆቹ አጥፊዎች ላይ እርምጃ ያለመውሰዱ ነው፡፡
የቀይ መስመሩ አጋዥነትና ተፈጻሚነት


አቶ ተሻለ እንደሚሉት፤ እስካሁን ያለው ሂደት የታችኛው ላይ ያነጣጠረ፣ የላይኛውን መደላድል ያልደፈረ ነበር፡፡ አሁን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በዚህ መልኩ ቆርጠው መነሳታቸው ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡ ሆኖም ጉዳዩ በኢህአዴግ የእድሜ ዘመን የማይነካ፣ ክልክልና የተጠበቀ ቀጠና ነው፡፡ ምክንያቱም የሙስናና መልካም አስተዳደር ጉዳይ አንድ ጊዜ ተሃድሶ፣ ሌላ ጊዜ ጥልቅ ተሃድሶ፣ አሁን ደግሞ ቀይ መስመር እየተባለ የዘለቀ ነው፡፡ ይህን ማለት ቀላል ነው፡፡ ነገር ግን ወደተግባር ሲገባ የማይነካ ቦታ ስለሚነካ ያንን መትቶ መጣልና ወደትክክለኛ መስመር ማምጣት በጣም ከባድ ነው፡፡


እንደ አቶ ተሻለ ገለጻ፤ ችግሩን መፍታት የሕዝብ ጥያቄን መመለስ ስለሆነም የእርሳቸው ቁርጠኝነትና መልካምነት ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን ችግሩን መፍታት ማለት አንድን ግለሰብ ህግ ፊት አቅርቦ እንደማስቀጣት ቀላል ያልሆነ የሥርዓትን መቀጣትና መታረም የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህን ያደረገ ሥርዓት መቀጣት የሚችለው ደግሞ ሽግሽጎችን በማድረግ አይደለም፡፡ ሕዝቡም እየጠየቀ ያለው ሽግሽግና ወንበር መቀያየር አይደለም፡፡ አሁን እርሳቸው ቀይ መስመር ማስቀመጣቸው መልካም ቢሆንም፤ ከፍትህ አካሉና ከመርማሪ ፖሊሱ ጀምሮ በአንድ ቋት ባለበት ሂደት ተጠያቂነት ያለበትን ግልጽና ቅንነት የተሞላበት አሰራርን በኢህአዴግ ውስጥ ለመፍጠር ስለማይቻል የተናገሩትን ለመተግበር ይከብዳል፡፡ ከሙስናና ከመልካም አስተዳደር ችግር የጸዳ ተቋም ለመፍጠርም የሚቻል አይሆንም፡፡


“ሕግ አስፈጻሚውም፣ ሕግ ተርጓሚውም፣ ሕግ አውጪውም ቢሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ የተዘፈቀ ይኖራል ተብሎ አይገመትም፤” የሚሉት አቶ ጉዑሽ በበኩላቸው፤ ሆኖም ችግሩን ለማቃለል ኃላፊነቱን ለሕዝብ መስጠት ተገቢ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ ሕዝቡ መድረክ እንዲያገኝና ነጻነቱ ተጠብቆለት እንዲናገር፣ የእርምጃ አወሳሰድ አቅጣጫዎችንም እንዲሰጥ መደረግ አለበት፡፡ ይሄም የሚሳካው እርምጃ የሚወስድ አካል ካለ ብቻ እንደመሆኑ፤ መጀመሪያ እርምጃ የሚወስደው ኃይል በራሱ መጽዳት ይኖርበታል፡፡


እንደ አቶ ጉዑሽ ገለጻ፤ እነዚህ ኪራይ ሰብሳቢዎች ጡንቸኞች ሆነዋል፡፡ ብዙ ፎቅ ሊሰሩና ብዙ ገንዘብም ሊያካብቱ ስለሚችሉም መንግሥትን ሊፈታተኑ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ችግሩን ለመከላከል አቅም የለም ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም መከላከያ፣ ፖሊስና ሌሎችን የጸጥታ አካላት ስላሉ አቅም አለ፡፡ ከኃላፊዎች ጀምሮ ተናብቦ መስራት ከተቻለ እርምጃ የማይወሰድበት ምክንያት አይኖርም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም ስንት ጠላት ያሸነፈ ሕዝብ እንደመሆኑ፤ ሙሰኞችን በቀላሉ ማሸነፍ አያቅተውም፡፡ ባጠቃላይ በመፈራራትና በምን ይሉኛል መተላለፍ ካልተፈጠረ በስተቀር አንድ ኃላፊ በትክክል ለሕዝቡና ለአገሪቱ ከቆመ እርምጃ የመውሰድ አቅም አያጣም፤ አለውም፡፡ በዚህ መልኩም ከተሄደ ሕዝቡ እርምጃ ከሚወስደው አካል ጋር ስለሚሰለፍ ችግሩን ማቃለል ይቻላል፡፡


“ድምጽ ሰርቀህ አሳልፈኝ ብሎ ካድሬውን ያንቀሳቀሰ መንግሥት፤ ለኪስህ የሚሆን ምንም መስረቅ አትችልም ማለት አይችልም” የሚሉት ዶክተር መረራ በበኩላቸው፤ አሁን ላይ አገሪቱን የሚያስተዳድረው የኢህአዴግ ትልቁ ችግርም ይሄው መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም ኢህአዴግ ዛሬ ላይ ችግሩን ማቃለል ያቃተው በዚህ መልኩ ድምጽ ሰርቆ እንዲያሳልፈው በመላ አገሪቱ ካድሬውን የቀሰቀሰ መንግሥት በመሆኑ፣ አሁን ላይ ተመልሶ ካድሬውን ለኪስ የሚሆን ገንዘብ አትስረቅ፤ ሰርቀህም ሀብት አታፍራ፤ የሚልበት አቅም ስላሳጣው መሆኑን ያብራራሉ፡፡


ዶክተር መራራ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለችግሩ መፍትሄና አቅጣጫ በዚህ መልኩ በሀሳብ ደረጃ ይዘው መቅረባቸው በጣም ጥሩ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም ያሳካላቸዋል የሚል ግምት የላቸውም፡፡ “ስርዓቱ የተመሰረተበት ዋና መሰረቱ ይሄው ስለሆነ ስራው ቀላል አይደለም” ሲሉም ምክንያታቸውን ያቀርባሉ፡፡ ይሄ ዝም ብሎ የሚናድ አይሆንም፤ ይህ ሲሆን ብዙ ጥቅሞችና የተሳሰሩ ነገሮች ስላሉ፤ የመተሳሰሪያ ክር የዘረጉ አካላት ከእርሳቸው የበለጠ ጉልበት ያካበቱበትም ሊሆን ስለሚችል ይሄን የማፍረስ ስራው ቀላል ጨዋታ የሚሆን አይደለም ሲሉም ሀሳባቸውን ያጠናክራሉ፡፡


መፍትሄ


“ችግሩን ለማቃለል ለሕዝብ ተጠያቂነት ያለው መንግሥት መፍጠር ነው” የሚሉት ዶክተር መረራ፤ ለዚህም በነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ሕዝቡ መሪዎቹን እንዲመርጥ ካልተደረገ፤ ሳይፈልግም ለማውረድ የሚችልበት ዴሞክራሲያው ስርዓት ካልተፈጠረ በስተቀር አንዳንድ እርምጃዎችን በመውሰድ፤ ባለስልጣናትን ቦታ በመቀያየር የሚለወጥ ብዙ ነገር እንደማይኖር ያብራራሉ፡፡ “በሕዝብ ድምጽ የተመረጠ መንግሥት፤ ሕዝብ ደግሞ ድምጹን ሲነፍገው የሚወርድ ፓርቲና መንግሥት ካልተፈጠረ በስተቀር አስቸጋሪ ነው፡፡ ሕዝብ ጥያቄ በጠየቀ ቁጥር ሰው መቀያየሩ ጫወታ ነው የሚሆነው፤” ይላሉ፡፡


አቶ ተሻለ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ በህገ መንግሥታዊ ጉዳዮችና አተገባበር ሂደቶች ዙሪያ አገራዊ መግባባት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ሕዝቡ መክሮ እንዲወስን እድል መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ይህ መንግስትና ስርዓት በሙስናና መልካም አስተዳደር ችግር በስብሷል፤ አርጅቷልም፡፡ በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት ቢሞክር ራሱን መስዋዕት ማድረግ ስለሚኖርበት ችግሩን እያወቀው ሊፈታ፣ መፍትሄ ሊሰጠውም አልቻለም፡፡ በመሆኑም ያገባኛል የሚል አካል ሁሉ በአንድ ጥላ ስር እንዲመክር በማድረግ የጋራ መግባባት እንዲፈጥር ማስቻል፤ ልዩነቶችን ለይቶም የመፍትሄ አቅጣጫ እንዲያስቀምጥና የጋራ መፍትሄ እንዲሰጥ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
“አሁን የመንግስት ውሳኔ መሆን የሚገባው ወይ አገርን አድኖ ራስን ማረም፤ ካልሆነም ራስን አስቀድሞ አገርን ማጥፋት ነው” የሚሉት አቶ ተሻለ፤ ችግሩ ስር ነቀል ለውጥና መፍትሄ የሚፈልግ እንጂ በጊዜያዊ ጥገና የእሳት ማጥፋት ስራ እየተከናወነ የሚፈታ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም ሕዝቡ ምንም እንኳን በባለቤትነት ስራውን መስራት የሚገባው ቢሆንም፤ መንግስት ለስራው ሙሉ ትብብር ሊያደርግ ይገባዋል፡፡ ይህ ሲሆን በመግባባት ችግሮቹን ማቃለል እንደሚቻል ይገልፃሉ፡፡


“በዚህ ዙሪያ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ብዙ ጊዜ ተናግረናል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነትና ኪራይ ሰብሳቢዎች ካልተወገዱ ተሰባስበው ጡንቸኞች ይሆናሉ፤ መንግሥትንም ይፈታተናሉ፤ አገሪቱን ወደችግር ይወስዳሉ በሚል አሳውቀናል፤” የሚሉት አቶ ጉዑሽ በበኩላቸው፤ “ሁሉም ሰው እጁ ስላለበት በሰዓቱና በወቅቱ እርምጃ መወሰድ አልቻለም፡፡ እኛም እንደጠላት እየተቆጠርን ነው ያለነው፡፡” ይላሉ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከመናገር፣ ለህዝቡ ከማሳወቅና ከህዝቡ ጎን ከመቆም ባለፈ ሚና እንደሌላቸው በመጠቆምም፤ አሁን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ መልኩ ቆርጠው ከተነሱ የሚበደለው ህዝብ፤ የሚዘረፈውም የአገሪቱ ሀብት እንደመሆኑ ሁሉም ህዝብ ከጎናቸው እንደሚቆም፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎችም እንደሚደግፏቸው ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን እንደቀደሙት ጊዜያት ፈራ ተባ የሚባል ከሆነ ስራው አስቸጋሪ እንደሚሆንም ይጠቁማሉ፡፡


እንደ አቶ ጉዑሽ ገለጻ፤ ቀደም ሲል አቶ መለስ ስለ ችግሩ ብዙ ጊዜ ይናገሩ ነበር፤ ነገር ግን ወደ ተግባር መግባቱን አልደፈሩም፡፡ በተመሳሳይ አቶ ኃይለማርያም ብዙ ጊዜ ተናግረዋል፤ ትናንሾቹን ከመነካካት ባለፈ ወደላይ አልዘለቁም፡፡ ዶክተር አብይም በቀደመው መልኩ ከሄዱ ስራው አስቸጋሪ ነው፡፡ ሆኖም በቆራጥነት ከተነሱ ከኢትዮጵያ ህዝብ በላይ ምንም ስለሌለ ከሙሰኞች በስተቀር ማንኛውም ዜጋ እርምጃውን ለማገዝ ከጎናቸው ይሰለፋል፡፡

ወንድወሰን ሽመልስ

Published in ፖለቲካ

ግብርና የአገሪቱ የኢኮኖሚ መሰረት ሆኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጨባጭ ለውጦች ቢያስመዘግብም፤ አሁንም ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ሸብበው ይዘውታል፡፡ አነዚህ ችግሮችም ግብርናው ከ70 በመቶ በላይ የአገሪቱ የወጪ ንግድ ገቢ ምንጭ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸውንም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ለመሆኑ የግብርናውን ምርትና ምርታማነቱንም ሆነ ወጪ ንግዱን ድርሻ ለማጎልበት ባለፉት ስምንት ወራት ምን ተሰራ? ምን ችግርስ አጋጠመ? ለቀጣይስ ምን ታስቧል? በሚሉና ተያያዡ ጉዳዮች ዙሪያ የቀድሞ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ዶክተር እያሱ አብርሃ ጋር ቆይታ አድርገን የሚከተለውን አጠናቅረናል፡፡
የተከናወኑ ስራዎች
የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር በተያዘው በጀት ዓመት ምርትና ምርታማነት በመጨመር ዋና ዋና የምግብ ሰብሎችን ምርታማነት ወደ 345 ሚሊየን ኩንታል ለማድረስ እቅድ ይዞ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በያዝነው የበልግ ወቅትም 1 ነጥብ 41 ሚሊየን ሄክታር መሬት ታርሶ 344 ሺህ 869 ሄክታር በዘር ለመሸፈን ቢቻልም፤ በተወሰኑ በልግ አብቃይ አካባቢዎች የዝናብ መዘግየት በመታየቱ ምክንያት አፈፃፀሙ ዝቅተኛ ሆኗል፡፡
ምርትና ምርታማነትን ለመጨመርና የአርሶ አደሩንም ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ የተለያዩ የአትክልት፣ የፍራፍሬና የስራስር ሰብሎች ምርጥ ዘር 2 ሚሊየን 247 ሺህ 24 ኩንታል ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡ ለወጪ ገበያ የሚሆን 76 ሺህ 950 የአቮካዶ ፍሬ ሰጪ ዝርያ ከውጪ ሀገር በማስመጣት በአራት ክልሎች ተሰራጭቶ የማዳቀል ስራ ተከናውኗል፡፡
ለስራዎቹ ስኬት የአርሶና አርብቶ አደሩ ጥረት የማይተካ ሚና ያለው በመሆኑ የኤክስቴንሽን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ቀዳሚው ስራ ተደርጎ በመሰራቱም የሞዴል አርሶ አደሮችን ቁጥር በአምስት በመቶ ማሳደግ ተችሏል፡፡ ባሉት 14 ሺህ 64 የአርሷደር ማሰልጠኛ ተቋማትም የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል፡፡ የተፋሰስ ልማት፣ የመሬት አጠቃቀም፣ የአፈር ለምነትና ጤንነትን የማሻሻል ስራዎችም የተከናወኑ ሲሆን፤ 627 ሺህ ሔክታር መሬት የተጎዱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ ተደርጓል፡፡
የምርምር አቅምን በማሳደግ የቴክኖሎጂና መረጃ አቅርቦትን ለማሻሻልም ባለፉት ስምንት ወራት 56 ቴክሎጂዎችንና መረጃዎችን ለማውጣት ተችሏል፡፡ በሰብል፣ በእንስሳት፣ በተፈጥሮ ሀብት፣ ግብርና ምህንድስና ለ37 ሺህ 580 አርሶና አርብቶ አደሮች እንዲሁም ባለሃብቶችን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ ለማድረግ ተችሏል፡፡ በቴክኖሎጂ ብዜት በሰብል ዘርፍ 3 ሺህ 804 ኩንታል መነሻ ዘር፣ 151 ሺህ 550 የተለያዩ ችግኞች ለተጠቃሚዎች ቀርቧል፡፡ በግብርና ሜካናይዜሽን በኩልም 223 የእርሻ መሳሪያዎች ተገዝተዋል፡፡
ለ2010/11 ምርት ዘመን 12 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ግዢ ተፈፅሞ 4 ነጥብ 4 ሚሊየኑ ወደ ክልሎች ተጓጉዟል፡፡ ባለፉት ስምንት ወራትም ምጥን ማዳበሪዎችን ለማስተዋወቅ ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች በ720 አርሶ አደሮች ማሳ ላይ የሰርቶ ማሳያ ተካሂዷል፡፡ በተገኘው ውጤትም ከሶስት እስከ 14 በመቶ የምርት ጭማሪ ተገኝቷል፡፡ በተመሳሳይ የህያው ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ተደራሽ በማድረግ 59 ሺህ ሔክታር መሬት በማልማት የጥራጥሬ ሰብሎችን ምርታማነት ከ30 እስከ 40 በመቶ ማሳደግ ተችሏል፡፡ የአፈር አሲዳማነት ችግር በሚታይባቸው አካባቢዎች 14 ሺህ ሔክታር አሲዳማ አፈር በከፍተኛ ስራ በመልማቱ ከፍተኛ የምርት ዕድገት በማሳየቱ ከምርት ውጪ የሆኑ የእርሻ መሬቶችን ወደ ምርት እንዲገቡ ለማድረግ ተችሏል፡፡
ከግብርናው ዘርፍ 40 በመቶ የውጪ ገቢውን የሚሸፍነው የቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ምርትና ምርታማነት ለማሻሻል በተሰራው ስራ በ16 ሺህ 860 ሄክታር መሬት የቡና ማሳ ለምቷል፡፡ በሻይ ልማቱም በኦሮሚያ ክልል በአርሶ አደሮች ተሳትፎ 500 ነጥብ 7 ሔክታር መሬት እየለማ ሲሆን ምርት ከሚሰጥ 200 ሔክታር መሬት ላይ 1 ሺህ ቶን እርጥብ አረንጓዴ ሻይ ቅጠል ማምረት ተችሏል፡፡ በቅመማ ቅመም ሰብሎች ልማትም በምርት ዘመኑ 361 ሺህ 603 ሔክታር መሬት በማልማት 545 ሺህ ቶን ተመርቷል፡፡
የወጪ ንግድ ገቢ ግኝት
ዘርፉ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ ከፍ ለማረግ የሚያስችል መሆኑ ታምኖ በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡ በዚህም የቅባት ሰብሎች በማቅረብ 306 ነጥብ 76 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ ይህ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመጠን 34 ነጥብ 4 በመቶ፣ በገቢ ደግሞ 52 ነጥብ 7 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ባለፉት ስምንት ወራት 538 ሺህ 563 ቶን የጥራጥሬ፣ የአገዳና ብርዕ ሰብሎችን ለውጪ ገበያ በማቅረብ 478 ነጥብ 53 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ተገኝቷል፡፡ ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመጠን 2 ነጥብ 64 በመቶ በገቢ ደግሞ 15 በመቶ ያክል ቅናሽ አሳይቷል፡፡ አልፎ አልፎ በተወሰኑ ሰብሎች ላይ ታይቶ የነበረው የዋጋ መቀነስና በአንዳንድ አገሮች የተጣሉ ተጨማሪ የታክስ ጥያቄዎች ለጉድለቱ ምክንያት ናቸው፡፡
ተግዳሮቶች
የአፈር ለምነት መመናመን፣ የአሲዳማነትና ጨዋማነት መስፋፋት፣ በአንጻሩ የአፈር ለምነትና ጤንነት ማሻሻያ ቴክኖሎጂዎች ያለመስፋፋት ግብርናውን እየተፈታተኑት ይገኛሉ፡፡ ተቋማዊ የማስፈፀም አቅምን የሚፈታተኑ የሰው ኃይልና የሎጂስቲክ እጥረት፣ በፌደራልና በክልሎች ደረጃ የተናበበ የአደረጃጀት ስርዓት አለመጠናከር፣ በዕፅዋት ጥበቃና ቁጥጥር፣ በአፈር ለምነት ማሻሻያ፣ መካናይዜሽንና የተናበበ የገጠር ስራ ዕድል ፈጠራ ያለመኖርም ተደማሪ ችግሮች ናቸው፡፡
የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከላት በተወሰኑ አካባቢዎች በተሟላ መልኩ አለመቋቋም፣ የተቋቋሙትም በውስጥ ቁሳቁስና በማስተማሪያ አጋዥ መሳሪያዎች አለመሟላት፣ በማዳበሪያ አጠቃቀም የመካናይዜሽን ተደራሽነት ስርዓትና አደረጃጀት ያልተዘረጋለት መሆኑ፣ በዘር ምርትና ግብይት ሂደት የፋይናንስ ብድር አቅርቦት ስርዓቱ ውስን መሆንም ተጠቃሽ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡
የመፍትሄ እርምጃ
የግብርናው እድገት ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችን በጥናት ለይቶ በበላይ አመራሮች ምላሽ እንዲሰጥባቸው ተደርጓል፡፡ በዚህም የሊዝ ፋይናንስ አገልግሎት እንዲፈቀድና የግብርና ኤክስቴንሽን መሳሪያዎች ከቀረጥ ነፃ ሆነው ከውጪ በስፋት እንዲገቡ የማድረግ ስራ መንግስት እያመቻቸ ነው፡፡ በተጨማሪም ከውጪ አገር የሚገቡ መዝሪያና የመውቂያ መሳሪያዎች ተሞክረው ግብረመልሱ አዎንታዊ በመሆኑ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በማዘጋጀት ለሌሎች ደጋፊ መንግስታት የድጋፍ ጥያቄ ቀርቧል፡፡
ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ጉልህ ድርሻ ላለው የቡና ምርት ላይ የሚያጋጥመው የህገወጥ ንግድና ዝውውርን ለመከላከልም ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ በዚህም በኬላዎችና በድንገተኛ የመንገድ ላይ ቁጥጥር 1 ሺህ 26 ነጥብ 723 ቶን ቡና ተይዞ ተወርሷል፡፡ ቀጣይነት ያለው መፍትሄ ለማምጣትም አቅርቦት ሽኝትና ክትትል ብሎም የላኪዎች የኮንትራትና የክምችት ክትትልና ቆጠራ እየተሰራ ይገኛል፡፡
የተባይ ክስተትን ከመከላከል አኳያም የዕፅዋት ጤናና ጥራት ቁጥጥር ስራን ለማሳደግና በሰብል ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የበረሃ አንበጣ በሚከሰትባቸው የኢትዮጵያ ሶማሊና አፋር ክልሎች በ36 ወረዳዎች 103 ሺህ 440 ሄክታር የአሰሳ ስራ በማካሄድ የመከላከል ስራ ተሰርቷል፡፡ በተያያዘ መደበኛ ተምችን ለመከላከል በተደረገው ጥረት በአራት ወረዳዎች በ319 ነጥብ 5 ሔክታር ላይ መከላከል ተችሏል፡፡
የአሜሪካ መጤ ተምች ላይ በሁሉም በቆሎ አብቃይና ተምቹ ሊከሰትባቸው በሚችልባቸው ወረዳዎች የአሰሳና የመከላከል ድጋፍ ተደርጓል፡፡ በስምንት ወራቶች ውስጥም በስምንት ክልሎች በ665 ሺህ 826 ሄክታር ላይ ተከስቶ 631 ሺህ 239 ሔክታር መሬት ላይ በባህላዊ ዘዴና በኬሚካል ለመከላከል ተችሏል፡፡ በመኸርና በመስኖ በሚለሙ በ17 ሺህ 555 ሄክታር መሬት ላይ ተከስቶ የመከላከል ስራ ተሰርቷል፡፡
በየዓመቱ በበልግና መኸር በሚለሙ ሰብሎች ላይ ጉዳት የሚያደርሰውን የግሪሳ ወፍ ችግርን ለመከላከልም የመራቢያ አካባቢዎችን በማጥናት የተከሰተውን 37 ነጥብ 76 ሚሊየን የሚገመት የወፍ መንጋ፤ እንዲሁም የስንዴ ዋግ በሽታንም በ22 ዞኖችና በሁለት ልዩ ወረዳዎች በአጠቃላይ በ117 ወረዳዎች ላይ በ229 ሺህ 271 ሔክታር ላይ በመከሰቱ በህዝብ ተሳትፎ መከላከል ተችሏል፡፡
በዘርፉ ፈጣንና ዘላቂነት ያለው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የአፈር ምርመራ ውጤት እንዲሁም የሰብል ንጥረ ነገር ፍላጎት ላይ የተመረኮዘ የማዳበሪያ አጠቃቀም ስርዓት ለመዘርጋት በአገር አቀፍ ደረጃ እስካሁን ከ80 ሺህ በላይ የአፈር ናሙና ተሰብስቧል፡፡
የትኩረት አቅጣጫ
በቀጣይም ምርትና ምርታማነትን በሚያሳድጉ በዘርፉ ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት ይሰራል፡፡ በዚህም ሁለንተናዊ አቅምን መገንባት፣ የመነሻ ዘር አቅርቦት ሁኔታን ማጠናከርና በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ የተመሰከረለት ዘር ማምረትን ማጠናከር፣ የግል ባለሀብቶችን ተሳትፎና ዕውቀት ማጎልበት፣ ለዘር ማምረት ሂደት የፋይናንስና የብድር አቅርቦት ስርዓቱን ማሻሻያ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡
በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈፃፀም ባለፉት ሁለት ዓመታት በዘርፉ ለውጦች እንዲመዘገቡ መደረጉ የሁሉም አካላት ርብርብ ውጤት መሆኑ ዕሙን ነው፡፡ በተደረገው ያላሰለሰ ጥረት የአየር መዛባት ያስከተለውን ተፅዕኖ በመቋቋም ዘርፉ ለአጠቃላይ ኢኮኖሚ ዕድገት ሊኖረው የሚገባውን ከፍተኛ ሚና እንዲጫወት ተደርጓል፡፡ የተያዘው ዓመትም ወሳኝ ምዕራፍ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

ፍዮሪ ተወልደ

Published in ኢኮኖሚ

እአአ 2011 በሶርያ ህዝባዊ አመፅ ከተነሳ በኋላ የኢራን ወታደራዊ ኃይል ቁጥር በሶርያ ውስጥ እየጨመረ ይገኛል፡፡ ሆኖም ህዝባዊ አመፁ በተነሳበት አካባቢ ኢራን በሶርያ ውስጥ የነበራት ጣልቃ ገብነት አነስተኛ ስለነበር ወታደሮቿን ለመላክ ዘግይታለች፡፡ በአሁን ወቅት ግን የኢራን ወታደሮች በሶርያ ምድር ቁጥራቸው እየበዛ እንዳለ የአልጀዚራ ዘገባ ይጠቁማል፡፡
እአአ 2013 በፀደይና በበጋው ወራት የተቃዋሚው ኃይል በሶርያ ውስጥ ብልጫ ወስዶ ነበር፡፡ ነገር ግን የኢራን ጦር ባደረገው ጥረት የአሳድ መንግስት መልሶ የኃይል ሚዛኑን መቆጣጠር መቻሉን ዘገባው ይጠቅሳል፡፡ እአአ 2014 ላይ የሽብርተኛው ቡድን አይ.ኤስ ከተመሰረተ በኋላ ነበር ኢራን በይፋ በሶርያ ውስጥ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በሚል ጣልቃ መግባት የጀመረችው፤ የወታደሮቿንም ቁጥር እያሳደገች የመጣችው፡፡ በዛው ዓመት መደበኛ ወታደራዊ ኃይል የኢስላሚክ አብዮት አራማጅ ፓርቲን ተቀላቀለ፡፡ በተጨማሪም የአፍጋኒስታን፣ የፓኪስታን እና የሊባኖስ ወታደሮች በአካባቢው መታየት ጀመሩ፡፡
እአአ 2015 በበጋው ወራት የአል.ቃይዳ ብርጌድ ኮማደርና የኢስላሚክ ለውጥ አራማጅ ፓርቲ ቀኝ እጅ ሜጀር ጄኔራል ኩሳምሶማኒ ሩስያን ጎበኙ፡፡ ከጉብኝቱ ሶስት ወራት በኋላ ሩስያ ወደ አካባቢው ወታደሮቿን ያሰማራች ሲሆን፤ ለአሳድ መንግስት የአየር ጥቃት ከለላ በመስጠት በሶርያ የአየር ድብደባ ማካሄድ ጀመረች፡፡ የኢራንና የሩስያ ጥምረት የአሳድን መንግስት ከመውደቅ መታደጉን ዘገባው ይጠቅሳል፡፡ ነገር ግን የሞቱ ወታደሮች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ሲደረግና ጦርነቱ ላይ ለመቆየት የሚደረገው ጥረት እየጨመረ ሲመጣ፤ የኢራን መንግስት ለዜጎቹ ስለ ሶርያ ጦርነት አስፈላጊነት ለመግለፅ እያዳገተው መምጣቱ ዘገባው ያሳያል፡፡
የሟች ወታደሮችን ቀብር ከህዝቡ መደበቅ
ኢራን በሶርያ ህዝባዊ አመፅ መሳተፍ የጀመረችው ገና ከጅምሩ ቢሆንም፤ የኢራን ባለስልጣናት ግን ጣልቃ ገብነቱ የተጀመረው የአይ.ኤስ የሽብርተኛ ቡድን ከተመሰረተ ጀምሮ መሆኑን እና የኢራን ወታደሮች በጦርነቱ ህይወታቸውን ማጣት የጀመሩት ከዚሁ ወቅት ወዲህ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እአአ ከ2016 በኋላ ከፍተኛ የጦር መሪዎችን ጨምሮ ጉዳት የደረሰባቸውና የሞቱት የኢራን ወታደሮች ቁጥር ከአንድ ሺ በላይ ደርሷል፡፡ በአሁን ወቅት ይህ ቁጥር በአራት እጥፍ መጨመሩን ዘገባው ያትታል፡፡ እአአ 2014 እና 2015 ላይ የአይ ኤስ የሽብርተኛ ቡድን በተለያዩ አካባቢዎች ከተስፋፋ በኋላ ነበር የኢራን መንግስት ወደ ሶርያ ወታደሮችን ሲያሰማራና ሲቀጥር ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ነው በሚል መግለጽ የጀመረው፡፡
ኢራን የጀመረችው የሽብርተኝነት መከላከል አሜሪካ ከምትመራው ቡድን ጋር ተመሳሳይ ነበር፡፡ በዚህም ምዕራባዊያን የአሳድን መንግስት ስልጣን ላይ በማቆየት አይ.ኤስን መዋጋት ይቻላል፤ የሚል አማራጭ እንደነበራቸው ዘገባው ይጠቅሳል፡፡ ነገር ግን የአሳድ መንግስትና አይ.ኤስ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች በመሆን የአሳድ ሙሰኛ ባለስልጣናት አይ.ኤስ እንዲፈጠር ምክንያት ሆነዋል፡፡ በዚህም ብዙ ንፁሀን ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
የኢራን መንግስት ለዜጎቹ ስለጉዳዩ ሲያስረዳ ኢራን በዋናነት በሶርያ ውስጥ መግባት የፈለገችው በደማስቆ ውስጥ የሚገኙ የሽሀ ተከታዮችን ከሽብርተኞች ለመጠበቅ መሆኑን ይገልፃል፡፡ በደቡባዊ ደማስቆ የሚገኘው ሳይዳ ዛይነብ መስኪድ የሽሀ ሙስሊም ቤትና የመጀመሪያው የሽሀ ኢማም አሊ ኢብን አቢ ታሊብ የነብዩ መሀመድ አማች ሴት ልጅ መቃብር ስፍራ መሆኑን ዘገባው ያመለክታል፡፡
በዛን ወቅት የኢራን የጦር አመራሮች በሶርያ ውስጥ የወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ሲያደርጉ በዋናነት የኢስላማዊ አብዮት ለመፍጠር ነበር፡፡ በተያያዘም እአአ 2015 የካቲት ወር ላይ የኢስላሚክ አብዮት ጠባቂ ቡድን መሪ ሱሊማን እንዳሉት፤ በአሁን ወቅት የኢስላም አብዮት በአካባቢው እየተቀጣጠለ ይገኛል፡፡ አብዮቱ ከባህሬን እስከ ኢራቅ እንዲሁም ከሶርያ፣ የመንና ሰሜን አፍሪካ ድረስ ተዳርሷል፤ ማለታቸውን ዘገባው ይጠቁማል፡፡
ኢራን የአሳድን መንግስት ለምን እንደምትጠብቅና ስላላት ጣልቃ ገብነት ከመናገር የተቆጠበች ቢሆንም አንዳንድ ባለስልጣናት ግን ደማስቆ ኢራን ከኢራቅ ጋር እአአ 1980 እስከ 1988 ድረስ በነበራት ጦርነት ላሳየችው ታማኝነት ብድር ለመመለስ ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡
በተቃራኒው የኢራቅና የኢራን ጦርነት ወቅት የሞቱ ወታደሮች በአደባባይ ታስቦ እንዲውል ስታደርግ በሶርያ ውስጥ ተሰማርተው ህይወታቸውን ላጡ ወታደሮች ግን ምንም አለመደረጉን ዘገባው ያሳያል፡፡ የኢስላሚክ አብዮት ጠባቂ ወታደሮች በከፍተኛ ሁኔታ በሶሪያ የሚሞቱ ወታደሮችን የሚያስቡበት ስርዓት ቢኖራቸውም ለህዝቡ ግን ግልፅ የተደረገ አለመሆኑን ዘገባው ይጠቁማል፡፡
ይህ ሁኔታ በአሁን ወቅት አስፈሪ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ተቀናቃኙ አያቶላህ ሆምኒ ‹‹በሂወት እያለንም ሀዘን ላይ ነን›› የሚል ንግግር ኢራን ከኢራቅ ጋር ጦርነት ከመጀመርዋ በፊት ተናግረው እንደነበር ዘገባው ያስታውሳል፡፡ ለአስርት አመታት በቀብር አከባበር ወቅት የኢስላሚክ ሪፐብሊክ ሽሀ የሀዘን ባህል ህዝቡ በተገኘበት እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ነገር ግን ኢራን በሶርያ ውስጥ እያደረገችው ያለው ጣልቃ ገብነት የሞቱትን ወታደሮች በአደባባይ ለማሰብ መዘጋጀት ለኢራን ባለስልጣናት ከባድ እንደሚሆንባቸው ዘገባው ያሳያል፡፡
ያልተገለፁ ወጪዎች
የአይ.ኤስ ሽብርተኛ ቡድን ከመመስረቱ ቀደም ብሎ ሶርያን መልሶ ለማቋቋምና ኢራን ኢኮኖሚውን ለመመለስ ለአሳድ መንግስት የወታደራዊ ድጋፍ እያደረገች ትገኛለች፡፡ ቃል በተገባው መሰረት ከወታደራዊው ዘመቻ የሚገኘው ትርፍ በአንፃራዊነት ሲታይ ጥሩ ይመስላል፡፡ ነገር ግን የሶሪያ ኢኮኖሚ የተረጋጋ ባይሆንም ሩስያ በዋናነት በምታደርገው ጣልቃ ገብነት ትርፍ ለማግኘት አላማ እንዳላት ዘገባው ያሳያል፡፡
የኢራን ባለስልጣናት አሁንም በሶሪያ ስለሚኖራቸው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እያወሩ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ግን በሶርያ እያወጡት ያለው ገንዘብ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እያቃወሰው ይገኛል፡፡ በሶሪያ ህዝባዊ አመፅ ጅማሮ ኢራን በሶርያ ውስጥ ብዙ ቢሊዮን ዶላር ያወጣች ቢሆንም ያወጣችውን ገንዘብ ለመመለስ ግን የተወሰነም ቢሆን እድል ያላት ይመስላል፡፡ በተጨማሪም ለአራት ሺ የሂዝቦላ ወታደሮች በሶርያ ላደረጉት አስዋፅኦ ክፍያ ይጠብቃሉ፡፡
ሶርያ እየወጣ ስላለው የወታደራዊ ወጪ ብዛት ለህዝብ ጆሮ እንዳይደርስ የተደረገ ቢሆንም ኢራን በሶርያ እያደረገችው ስላለው ተጋድሎ ግን እስካሁን ግልፅ የሆነ ነገር የለም፡፡ ኢራን ከስድስት ቢሊዮን ዶላር እስከ 20 ቢሊዮን ዶላር በዓመት ለወታደራዊ ወጪ እንደምታደርግ ዘገባው ያሳያል፡፡ አላግባብ የሆነው ወጪ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ እያዛባ መሆኑን ዘገባው ያትታል፡፡
በአይ.ኤስ ላይ በተገኘው ድል የይገባኛል ጥያቄ
የሞቱ ሰዎችን ወደ አገራቸው መመለስና ለሶሪያ መንግስት ድጋፍ ማድረግ የኢራን መንግስት ለህዝቦቹ ለማስረዳት የከበደው ይመስላል፡፡ ህዝቡን ለማሳመን በድንበር አካባቢ ያሉትን ድሎች ማግኘት ይፈልጋል፡፡ ይህ ጉዳይ በወቅቱ ብዙም አስገራሚ አይደለም፤ እአአ 2017 የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይዳር አል አባዲ በኢራቅ ከአይ.ኤስ ጋር የተደረገው ጦርነት ማብቃቱን አስታወቆ ነበር፡፡ በተመሳሳይ የሩስያ ጦርም በሶሪያ የነበረውን የአይ ኤስ ጦር ማስወጣቱን ተናግሯል፡፡ የኢራን የጦርና የፖለቲካ ምሁራን ስለ ጉዳዩ ከሶስት ሳምንታት በፊት ገልፀው እንደነበር ዘገባው ያስታው ሳል፡፡
ባሳለፍነው ህዳር ወር የኢራን መንግስት በከፍተኛ ሁኔታ በአይ.ኤስ ላይ ድል መቀዳጀታቸውንና ለዚህም የኢራን ወታደሮች አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው ነበር፡፡ ይህንም ጉዳይ ካያሀን የተባለው ወግ አጥባቂ ጋዜጣ በፊት ገፁ ማስፈሩን ዘገባው ይጠቅሳል፡፡ ከፍተኛ የኢስላም ሪፐብሊክ አመራሮች በአይ.ኤስ ላይ የመጣውን ድል በከፍተኛ ደስታ ሲያከብሩ ነበር፡፡ የኢስላሚክ አብዮት ጠባቂዎች መሪ ሶሎማኒ ለከፍተኛው የኢስላም መሪ ግልፅ ደብዳቤ የፃፉ ሲሆን፣ በደብዳቤውም በአይ ኤስ ላይ የተቀዳጁት ድል የኢራን ሻሂ ወታደሮችና የሂዝቦላ ጥረት መሆኑን መግለፃቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
በአይ ኤስ ላይ የመጣውን ድል ለመመዘን ቢሞከር የኢስላሚክ ሪፐብሊክ ጦር ኃይል ከነበረው የሰው ሀይል ያነሰ አልነበረም፡፡ የኢስላሚክ ሪፐብሊክ ጠባቂ ኮማንደር ሱሊማን በፕሬዚዳንት ሀሰን ራውሃኒ ሙገሳ ተችሮታል፡፡ ነገር ግን በአሁን ወቅት አይ.ኤስ ተሸንፏል፡፡ ኢራንም ለዜጎቿ በሶሪያ የምትቆይበት ምን ምክንያት እንዳላት መናገር አትችልም፡፡ የኢራን ዜጎች ትግስት እያለቀ ይመስላል፡፡ በዚህም ምክንያት ወታደራዊ ንቅናቄ የማድረግ ሁኔታዎች እየታዩ መሆኑን ዘገባው ይጠቅሳል፡፡

መርድ ክፍሉ

Published in ዓለም አቀፍ

ሀገራችን ቀደምት የሰው ልጅ መፈጠሪያ ብቻ ሳትሆን የበርካታ ክንውኖችም መሰረት ናት፡፡ በተለይ ለአፍሪካ የበርካታ ታሪኮች መነሻ በመሆን ትታወቃለች፡፡ ከነዚህም ውስጥ ስፖርት አንዱ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ እነ ፈረስ ጉግስ፣ ገበጣ፣ የገና ጨዋታ እና የመሳሰሉ ባህላዊ ስፖርቶች በኢትዮጵያ ቀደምት ታሪክ እንዳላቸው የተለያዩ ድርሳናት ይገልፃሉ፡፡ አሁን በዘመናችን የዓለምን ቀልብ እየገዙ ከሚገኙ ስፖርታዊ ክንውኖች አንዱና ዋነኛው በሆነው እግር ኳስም ቢሆን ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን በመመስረት ግንባር ቀደም መሆኗ ይታወቃል፡፡
ያም ሆኖ ግን ይህ ታሪካችን ቀስ በቀስ እየተቀዛቀዘ መጥቶ ብዙዎች አልፈውን ሊሄዱ ተገደዋል፡፡ የአፍሪካ ዋንጫን የመሠረተችውና ይህንን ዋንጫ አንድ ጊዜ የግሏ ማድረግ የቻለችው ሃገራችን አሁን አሁን በዚህ ዋንጫ ጨዋታ ላይ ለመሳተፍ እንኳን የሚያስችል ውጤት ማስመዝገብ ተራራ ከሆነባት ሰነባበተ፡፡
ለአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውና በወቅቱ ለነበሩ ተጨዋቾች ምስጋና ይግባቸውና ከአምስት ዓመት በፊት ከ31 ዓመታት ቆይታ በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ የመሳተፍ እድሉን ብናገኝም ይህም ቢሆን ጠንካራ መሰረት ላይ ያልተገነባ በመሆኑ መልሶ ተንዷል፡፡ እናም እግር ኳሳችን ከበሽታው ሳያገግም “አንድ እርምጃ ወደ ፊት፣ ሁለት እርምጃ ወደ ኋላ” እየሆነ እነሆ የኋሊት ጉዞውን ተያይዞታል፡፡ ይባስ ብሎ አሁን አሁን እግር ኳሳችን ላይ የተጋረጠው አደጋ ደግሞ ከኳሱ አልፎ የሃገራዊ ሠላማችን አደጋ ወደ መሆንም ተሸጋግሯል፡፡ ዛሬ ይህንን አስተያየት እንድሰጥ ያነሳሳኝም ጉዳይ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
የስፖርታዊ ውድድር ዋና ዓላማ በአካሉ የዳበረ፣ በአዕምሮ የበለፀገና በስነምግባሩ የታነፀ ብቁ ዜጋን ማፍራት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ የተነሳ በስፖርት ሜዳዎች ላይ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሠላም፣ መተሳሰብ፣ አንድነትና ፍቅር የጋራ እሴቶቻቸው ናቸው፡፡ የስፖርት መርህም ይህንኑ መሰረት ያደረገ ነው፡፡
ያም ሆኖ ግን በሃገራችን በስታዲዮሞች አካባቢ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጨመረ የመጣው የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ችግር ከስፖርቱም በዘለለ ሃገራዊ ሰላምን የሚያናጋ አደጋ እየሆነ መጥቷል፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ባለፈው ሳምንት ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲና መከላከያ እግር ኳስ ክለቦች ባካሄዱት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ላይ የታየው በአደባባይ ዳኛን የመደብደብ ድርጊት ትልቅ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ በርግጥ ይህ ድርጊት ለሃገራችን አዲስ አይደለም፡፡ ከዚያ ቀደም በወልዲያ የተከሰተው ተመሳሳይ አስነዋሪ ድርጊትና ሌሎቹም በአዲስ አበባ ስታዲየምና በሌሎችም እግር ኳስ ሜዳዎች ላይ እየጎሉ የመጡ የስነምግባር ችግሮች የዚሁ የተበላሸ ድርጊት አካላት ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ አሁን ከደረሰበት ደረጃ አንፃር ስንመለከተው ይህን ያክል ለፀብ መንስኤ ሊሆን የሚያስችል ምን ችግር አለበት የሚለውን ማየት ይገባል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በስፖርቱ ከመዝናናት ይልቅ ከስፖርቱ ጋር ተያይዞ በሚፈጠሩ ፀቦችና የስነምግባር ጉድለቶች የሚታዩትን ግጭቶች አይቶ የሚበሳጨው ይበልጣል፡፡ ስፖርቱም ከጠቀሜታው ይልቅ ጉዳቱ እያመዘነ መምጣቱን ያሳየናል፡፡ ለዚህ ችግር ዋነኛ መንስኤ እና ተጠያቂዎችም የተለያዩ አካላት ናቸው፡፡
በኔ እምነት የመጀመሪያው ተጠያቂ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሃገራችን ከደረሰችበት የፖለቲካ ስልጣኔ እና እመርታ አንጻር ሲታይ ገና በርካታ ርቀቶችን ወደ ኋላ የቀረ መሆኑን በቀላሉ ማየት ይቻላል፡፡ ሃገርን የመምራት ትልቅ ሃላፊነት የተጣለባቸው የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር በሃገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ለተከሰተው የህዝብ ቅሬታና አለመረጋጋት የመፍትሄው አካል ለመሆን በሚል ምክንያት ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው በተነሱባትና በአጭር ጊዜ ስልጣናቸውን ለሌላ አመራር ባስረከቡበት ሃገር ውስጥ ሆነን ከአንድ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራርነት መልቀቅ ትልቅ ዳገት የሆነበት ምክንያት በዚያ አካባቢ ምን አለ? የሚል ጥያቄ በትልቁ ያጭራል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በራሱ ውስጥ የሚታዩትን ችግሮች መፍታት አቅቶትስ እንዴት እግር ኳሱን ሊያስተዳድርና ሊመራ ይችላል? አንድ ቤተሰብ ጠንካራ እና ዓላማ ያለው የሚሆነው ቤተሰቡን የሚያስተዳድረው አባት ወይም እናት ጠንካራ ሲሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን እናትና አባት ተስማምተው ቤተሰብ መምራት ካቃታቸውና ጠዋትና ማታ የሚጨቃጨቁ ከሆነ የዚያ ቤተሰብ አባላትም በሠላም ሊኖሩ አይችሉም፡፡ ልጆችም በሠላም ሊያድጉ አይችሉም፡፡ ከእንዲህ አይነት ቤተሰብ ጥሩ ስነምግባር ያላቸውና አርዓያ የሆኑ ልጆችንም መጠበቅ አይቻልም፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም አሁን በሃገሪቱ ለተፈጠረው የሜዳ ላይ ስነምግባር ጉድለት ማንንም ተጠያቂ ሳያደርግ ሃላፊነቱን ሙሉ ለሙሉ መውሰድ አለበት፡፡ እሱ ራሱን ለመምራት ሳይችል ቀርቶ እንዴትስ ሌሎች ክለቦችን ማስተዳደር ይቻለዋል? የፌዴሬሽኑን አመራር አካላት ለመምረጥ ከአንድም ለአራተኛ ጊዜ ”የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ” እያለ ጊዜውን የሚያጓትተውና እዚያው ቁጭ ብሎ የሚታትረው ይህ ፌዴሬሽን በዚህ ድርጊቱ ሊያፍር ይገባዋል፡፡ ሀገርን የሚያክል ትልቅ አካል ማረጋጋት በተቻለበት የሃገራችን ነባራዊ ሁኔታ አንድን የእግር ኳስ ፌዴሬሽን “እኔ ካልመራሁ ሞቼ እገኛለሁ” ማለት ከምን የመነጨ እንደሆነ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡አሁን ባለው ሁኔታ ይህ ችግር ከቀጠለ ደግሞ ሃገራችን ለፊፋ ቅጣት ልትዳረግ የማትችልበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ይህ ደግሞ የባሰ ኃላፊነትን ያለመሸከም ከፍተኛ የራስ ወዳድነት መገለጫ ነው፡፡
በርግጥ የኢትዮጵያ እግር ኳስ የተወሰኑ የፌዴሬሽኑ አመራሮች ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ስለእግር ኳስ ሲነሳ ሁላችንም ይመለከተናል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሃገራችን የተገነቡት ስታዲየሞች የህዝብ ንብረት ናቸው፡፡ ይህ ገንዘብ ደግሞ ከእያንዳንዳችን ኪስ የወጣ ነው፡፡ እነዚህ እግር ኳስ ስታዲየሞች ሲገነቡም በአንድ በኩል ሃገራችን በስፖርታዊ ውድድሮች በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ሃገራችንን የሚያስጠሩ ስፖርተኞችን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአዕምሮ የበለፀገ፣ በአካሉ የዳበረና ጤናማ ማህበሰብ በማፍራት ለነገዋ በማደግ ላይ ላለችው ኢትዮጵያ ዋስትና የሚሆኑ ዜጎችን ለማፍራት ነው፡፡
ያም ሆኖ ግን አሁን አሁን ይህ እግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ ከሰላማዊ የመጫዋቻ ሜዳነት ወደ ቦክስ ማጫወቻ መድረክ የተለወጠ እስኪመስል ድረስ ድብድብ የሚታይበት የነውጥ ቦታ እየሆነ መጥቷል፡፡ ከዚህ ቀደም የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ግጭት የሚፈጥሩበት አዲስ አበባ ስታዲየምም አሁን አሁን ተሞክሮው እየተቀመረና እየሰፋ መጥቶ ወደ ተለያዩ ስፖርት ሜዳዎችና ክለቦችም ተሸጋግሯል፡፡ ባለፈው ሳምንት በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲና መከላከያ ፣ቀደም ሲልም በወልድያና ፋሲል ከነማ ጨዋታዎች ላይ የተመለከትነውም ድርጊት እግር ኳሳችን ሙሉ ለሙሉ አቅጣጫውን ስቶ ባለቤት አልባ መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡
ከሁሉ በላይ አሳዛኙ ጉዳይ ደግሞ አሁን አሁን በእግር ኳስ ሜዳዎች እየታየ ያለው ችግር አቅጣጫውን ስቶ ፖለቲካዊ መልክ መያዙ ነው፡፡ በተለይ ከክልል ክልል የሚደረጉ ጨዋታዎች በዘር ላይ የተመሰረተ ግጭት የሚያስተናግዱ እየሆኑ መምጣታቸው አሳሳቢ ብቻ ሳይሆን አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጠው የሚገባ ችግር ሆኗል፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት በሃገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ ከነበረው ግጭት በስተጀርባ የተለያዩ ፀረ ሠላም ሃይሎች እንደነበሩ በተደጋጋሚ ሲገለፅ የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ሃይሎች ሃገራችን ተረጋግታ ማየት አይፈልጉም፡፡ በዚህ የተነሳ የማትረጋጋበትን መንገድ መፈለግ የዘወትር ሥራቸው ነው፡፡
ያም ሆኖ ግን ሃገራችን ከአንድ ወር ወዲህ ለሌሎች አርኣያ በሚሆን መልኩ ሠላማዊ ስልጣን ሽግግር ማካሄድ ችላለች፡፡ ይህ የስልጣን ሽግግር ደግሞ ለብዙዎቹ የኢትዮጵያን ሠላም ለማይፈልጉ አካላት አልተዋጠላቸውም፡፡ ይህንንም ፍላጎታቸውን በተለያዩ ማህበራዊ ድረገፆች እየለጠፉ ሠላማችንን ለማደፍረስ ጥረት አድርገዋል፡፡
ቀድሞውንም ቢሆን ምክንያታዊ የነበረው የሃገራችን ህዝብ ጊዜ መስጠት ተገቢ መሆኑን በመገንዘብ ሠላምን መርጦ ፊቱን ወደ ልማቱ እያዞረ ይገኛል፡፡ በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች ተከስቶ የነበረው ሁከትና ብጥብጥም ተቀርፎ ሠላም ሰፍኗል፡፡ ነገር ግን ይህ ሠላም ያልተመቻቸው የተለያዩ አካላት አሁን ሌላ አቋራጭ እየፈለጉ ዳግም የሃገራችንን ሠላም ለማደፍረስ አዲስ አቅጣጫ መከተል ጀምረዋል፡፡ ለዚህ ምቹ ሆኖ የተገኘው ደግሞ እግር ኳስ ሜዳ ስለመሆኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከሰቱ ያሉት ሁከቶችና ግጭቶች ማሳያ ናቸው፡፡
ሌላው በዚህ አጋጣሚ ሳልጠቅስ የማላልፈው ጉዳይ የሃገራችን የስፖርት አደጋገፍ ስርዓት ነው፡፡ የሃገራችን የስፖርት አደጋገፍ አስገራሚና አሳዛኝም ነው፡፡ በተለይ ከውጭ ስፖርት ጋር ተያይዞ ያለው የአደጋገፍ ስርዓት አንዳንዴ ትዝብት ውስጥም የሚጥለን ነው፡፡ ከነዚህም ውስጥ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በሃገራችን ከፍተኛ ደጋፊ ያላቸው እንደሆኑ ጨዋታ በተካሄደ ቁጥር በከተማችን ያለውን እንቅስቃሴ ማየት በቂ ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ ጠዋት በየታክሲው እና አውቶቡሱ ውስጥ የመጀመሪያው የኤፍ ኤም ሬዲዮዎኖቻችንና የርስ በርስ ጨዋታዎቻችንም ርዕስ ይህ እየሆነ መጥቷል፡፡
በሃገራችን የሚገኙ የስፖርት ደጋፊዎች ግራ መጋባት ውስጥ ያሉ ይመስለኛል፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያቴ ማንን እንደሚደግፉና እንዴት እንደሚደግፉ በግልፅ አለማወቃቸው ነው፡፡ አንዳንዶቹ ደጋፊዎች ልባቸው ያለው አውሮፓ፤ በተለይ እንግሊዝና ስፔን ነው፡፡ የነዚህ ደጋፊዎች ሁኔታ ሲታይ በአንድ በኩል በሃገራችን ያለው እግር ኳስ አለማደግ ወደ ውጭ እንዲያዩ የገፋፋቸው ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ አሁን አሁን በሁሉም ነገር የውጭውን ከመናፈቅ የመነጨ አባዜ ሊሆን ይችላል፡፡
“በዚህ የጨዋታ ዘመን እከሌ የሚባለውን ተጫዋች እንገዛለን! ይህንን ዋንጫ እንወስዳለን! ይህንን አሰላለፍ መከተል አልነበረበትም” ወዘተ የሚሉ የኔነት ስሜት የተጫናቸው አስተያየቶችን ከነዚህ የውጭ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች መስማት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ከዚህም አልፎ በዚህ መካከል በሚነሱ ግጭቶች ዱላ መማዘዝ የተለመደ ሆኗል፡፡ እኛን ቀርቶ አገራችንንም በቅጡ የማያውቁትን ክለቦችና ተጨዋቾች እያነሳን በኔነት ስሜት ውስጥ አስገብተን ለነሱ ከፍተኛ መስዋዕትነት ጭምር መክፈላችን ያስገርመኛል፡፡
አንድ ወቅት ያጋጠመኝን በዚህ አጋጣሚ ላካፍላቸሁ፡፡ እለቱ ቅዳሜ ነው፡፡ ምሽት ሁለት ሰዓት አካባቢ ይሆናል፡፡ አንድ የሰፈራችን ወጣት ከእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች አንዱ ደጋፊ በመሆኑ የእለቱን ጨዋታ ይከታተላል፡፤ ነገር ግን በእለቱ እሱ የሚደግፈው ክለብ አልተሳካለትም፡፡ እናም በዚህ መካከል በእለቱ አሸናፊ ከነበረው ክለብ ደጋፊ ጋር እሰጣገባ ውስጥ ይገባሉ፡፡ በመጨረሻም ፀቡ ተካሮ ወደ ቡድን ፀብ ይለወጣል፡፡ በእለቱ በዚህ ሁኔታ በተነሳው ፀብ ከአስር በላይ ወጣቶች ከፍተኛ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በመቶ ሺህ የሚቆጠር ንብረትም ወድሟል፡፡ በርግጥ ይህ የሁላችንም መገለጫ አይደለም፡፡ ሆኖም እንዲህ አይነት ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉ ወጣቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ እናም ይህ ለወደፊቱ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
ወደ ተነሳሁበት የአገራችን እግር ኳስ ሜዳ ልመለስ፡፡ በኢትዮጵያ ከኳሱ በላይ እያደጉ የመጡት የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳዎቻችንና ፀቦቻችን ናቸው፡፡ አሁን አሁን በሁሉም የሃገራችን ክልሎች እየተገነቡ ያሉትን እግር ኳስ መጫወቻ ሜዳዎች ስንመለከት ፈረሱ ከጋሪው መቅደሙን ያሳዩናል፡፡ በዚህ አይነት ሁኔታ አንድም እርምጃ መራመድ ላቃተው እግር ኳስ ከፍተኛ በጀት አውጥቶ ዘመናዊ ሜዳዎችን መስራት ትርፉ ለምንድነው ያስብላል፡፡ በዚህ ብር የታዳጊ ፕሮጀክት ቢገነባና ከስር ጀምሮ እያሳደጉ ማምጣት የተሻለ ይሆን እንደነበር አስባለሁ፡፡
እግር ኳስ ተጨዋቾቻችንም ትልቅ ራዕይ ሰንቀው የሚጓዙ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ እግር ኳሳችን የአፍሪካ ብሎም የዓለም ዋንጫን እንዲያነሳ ለምን መስራት አቃተን? ይህን ለማድረግስ ምን ይጎድለናል? የጥንት አባቶቻችን የነበሩበትን የከፍታ ማማ ለመንካት የሚያግደን ምንድነው? ምንም የለም፡፡ ስለዚህ ለዚያ አልሞ መነሳትና ያለምንበት ቦታ ለመድረስ መትጋት ተገቢ ነው፡፡
ያም ሆኖ ግን በሰበብ አስባቡ እግር ኳስ ሜዳ ውስጥ አምባጓሮ መፍጠርና የህብረተሰቡን ሠላም መንሳት ስፖርትን ከሠላማዊ ሜዳነት ወደ ጦርነት ቀጣና የሚሸጋግር በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በዚህ ጉዳይ ራሱን ማስተዳደር ያቃተው እግር ኳስ ፌዴሬሽን ችግሩን መፍታት ካቃተው መንግሥት ጣልቃ መግባት አለበት፡፡ ምክንያቱም አሁን እየተፈጠረ ያለው ከፌዴሬሽኑ ቁጥጥር ወጥቶ ሃገራዊ ሠላምን የማደፍረስ ጉዳይ ሆኗል፡፡
በተለይ እንዲህ ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል ተዘዋውሮ ለመጫወት አዳጋች እስኪሆን ድረስ የሚፈጠሩ አምባጓሮዎች ዘርፉን የሚያስተቹ ብቻ ሳይሆን መንግሥትም ቆም ብሎ እንዲያስብበት የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ ይህ ቀጣይ የቤት ሥራ ከአሁኑ ካልተሰራ ነገ ከዚህ ቀደም እንደተከሰተው ሃገራዊ ሁከት አድማሱ የማይሰፋበትና አቅጣጫውን የማይስትበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ስለዚህ ከዚህ በላይ ትዕግስት አደጋን የሚያስከትል በመሆኑ ችግሮችን ከመሰረታቸው ለይቶ ከወዲሁ መፍታት ይገባል፡፡

ውቤ ከልደታ

Published in አጀንዳ

አገራችን ባለፉት 15 ዓመታት ተከታታይ ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ የጀመረችውን የዕድገት ጎዳና በአግባቡ እየተጓዘች እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ምንም እንኳን ባለፉት ሁለት ዓመታት የሰላምና የመረጋጋት ችግሮች ቢያጋጥሙም መንግሥት በወሰደው ብልህ እርምጃ እየተቀረፉ ይገኛሉ፡፡
በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ለተፈጠረው የኅብረተሰብ ቅሬታና በዚህም ሳቢያ ለተነሳው ሁከትና ብጥብጥም ዋነኛ መንስኤ የነበሩት የአገልግሎት መጓደልና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች እንደነበሩ መንግሥት ባካሄደው ግምገማ አረጋግጧል፡፡ ችግሩንም ለመፍታት በየደረጃው የእርምት እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም የካቢኔ አባላትን በአዲስ መልኩ በማጠናከር ሥራቸውን የጀመሩ ሲሆን በአገራችን ተከስቶ የነበረው የሠላም መደፍረስ ችግርም ሊረግብ ችሏል፡፡
ያም ሆኖ ግን አሁን ባለው ሁኔታ የህብረሰተቡ ችግሮች ገና ያልተፈቱ በመሆናቸው የሚወሰዱ እርምጃዎች መቀጠልና ሌሎች ችግሮች እንዳይፈጠሩም ተገቢውን አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድ ይገባል፡፡ በተለይ አንዳንድ ችግሮች ህብረተሰቡን በማማረር ህዝቡ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ ሆን ተብለው ሠላምን በማይፈልጉ አካላት የሚፈጠሩ ችግሮች ናቸው፡፡ እነዚህን አካላት ለይቶ ተገቢውን እርምት መውሰድ ከመንግሥት ይጠበቃል፡፡
በአዲስ አበባና በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ሰሞኑን የተፈጠረው የዋጋ ጭማሪም ከወዲሁ ሊፈተሽና ፈጣን የማስተካከያ እርምጃ ሊወሰድበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ ህብረተሰቡ በየዕለቱ ከሚገለገልባቸው የምግብ ሸቀጦች አንጻር የሚፈጠሩ የዋጋ ንረቶች የኅብረተሰቡን አቅም በመፈታተን በቀላሉ እንዲማረር ያደርጋሉ፡፡ ከዚህ አንጻር በተለይ በዳቦ ላይ የተከሰተውን የዋጋ ጉዳይ ማጤን ተገቢ ነው፡፡
በተለይ በዳቦ ዋጋ ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ በርካታ ዜጎችን እያማረረ ያለ መሠረታዊ ችግር ነው፡፡ በአንድ ጊዜ እስከ 25 ከመቶ የሚደርሰው ይህ ጭማሪ በአንድ በኩል የጭማሪው ወጥ አለመሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በስንዴ ላይ የተጨመረውና በዳቦ ላይ የተደረገው ጭማሪ በግልጽ በማይታወቅበት ሁኔታ ኅብረተሰቡ እንዲማረር መንስኤዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ምንም እንኳን በሃገራችን ያለው የገበያ ሁኔታ ውድድር ላይ የተመሰረተ ቢሆንም ቅጥ ያጣ እንደሆነ በርካቶች የሚመሰክሩት ሃቅ ነው፡፡ ለምሳሌ ከጥቂት ወራት በፊት መንግሥት ያደረገውን የውጭ ምንዛሪ ማስተካከያ ተከትሎ ከውጭ የሚመጡ ምርቶች ላይ ብቻ ሳይሆን እዚሁ አጠገባችን የሚመረቱ እና ከውጭ ምንዛሪ ጋር ምንም አይነት ንክኪ የሌላቸው ምርቶች ላይ ከተደረገው የውጭ ምንዛሬ ማስተካከያ በላይ ጭማሪ ሲደረግ ተስተውሏል፡፡
በአገራችን ከዋጋ ጭማሪ ጋር ተያይዞ የሚደረጉ የዋጋ ጭማሪዎች ምንም አይነት ምክንያት የሌላቸውና ነጋዴውም ቢሆን ምን ያክል ወጪ እንደሚያወጣ እና ከዚህ በተጨማሪ ምን ያህል እንደሚያተርፍ ስሌት የማይሰራበት እንደሆነ ሸማቹ ያማርራል፡፡ በዚህ የተነሳ አንዳንድ ነጋዴዎች በአንድ ጊዜ ከመቶ በመቶ በላይ ትርፍ የሚያገኙበት ሁኔታም ይታያል፡፡
የሚደረጉ የዋጋ ጭማሪዎችም ምንም አይነት ምክንያት ላይ ያልተመሰረቱ በመሆናቸው አንድ ጊዜ ወደ ላይ ከወጡ ወደታች የማይመለሱበት ሁኔታ ይታያል፡፡ ይህ ደግሞ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበትን ለማምጣት በር የሚከፍት በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበዓለ ሲመታቸው ዕለት ባደረጉት ንግግር የዋጋ ንረቱ ማህበራዊ ቀውስ እንዳያስከትል ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡ ስለዚህ አሁን የተፈጠረው የዋጋ ንረት ተባብሶ ከፍተኛ የህዝብ ቅሬታና ምሬት ከመፍጠሩ በፊት ማስተካከል ተገቢ ነው፡፡
የንግድ ሥራ ራስን የምንጠቅምበት ሥራ ብቻ አይደለም፡፡ ራሳችን ተጠቅመን ሌሎችንም የምናገለግልበት ሥራ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ሥራ ላይ የተሰማራ የንግዱ ማህበረሰብ ሁሉ ከሚያገኘው ትርፍና ኪሳራ ጀርባ የሚያገለግለው ወገንና ህዝብ መኖሩን ማገናዘብና ለአገሩ ዕድገትና ሠላም የራሱን አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
በተለይ አሁን የምንገኝበት ወቅት የምርት ዘመኑ የግብርና ምርት ተሰብስቦ ለገበያ የሚቀርብበት ጊዜ ነው፡፡ በሌላ በኩል በያዝነው የምርት ዘመን ከፍተኛ የግብርና ምርት የተገኘበት ዘመን እንደሆነም ቀደም ሲል የተደረጉ ትንበያዎች ያሳያሉ፡፡ ከዚህ አንጻር አሁን በተለይ በግብርና ውጤቶች ላይ እያጋጠመ ያለው የዋጋ ንረት ሰው ሰራሽ እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡ ይህ ደግሞ ተገቢው ጥናትና ምርመራ ተካሄዶ መስተካከል አለበት፡፡
በሌላ በኩል በሃገሪቱ ገበያን ለማረጋጋትና እንዲህ አይነት ችግሮች ሲፈጠሩ ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ልዩ ልዩ ሸቀጣ ሸቀጥ እንዲያቀርቡ የተቋቋሙት የሸማቾች የኅብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖችም ተገቢውን ግልጋሎት እየሰጡ ባለመሆኑ በተለይ በዚህ ወቅት የተጣለባቸውን ሃላፊነት ሊወጡ ይገባል፡፡
የሚመለከታቸው የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮዎችና የንግድ ሚኒስቴርም እንዲህ አይነት ጭማሪዎች ሲከሰቱ ጊዜ ሳይሰጥ ችግሩን መፈተሽና የእርምት እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡ በተለይ አላግባብ የዋጋ ሸቀጦችን የሚደብቁና የዋጋ ንረት እንዲከሰት የሚያደርጉ፣ በገበያ አካባቢ የተሳሳቱ መረጃዎችን የሚነዙ፣ በአቋራጭ ለመክበር ሲሉ ከልክ በላይ ዋጋ የሚያንሩ እና መሰል ሁከት ፈጣሪዎችን ተከታትሎ የእርምት እርምጃ መውሰድ ይገባል፡፡
ይህ ካልሆነ ግን አሁን ባለው ሁኔታ የሚከሰተው ችግር ሁሉንም የሚጎዳ ነው፡፡ በተለይ አሁን በተፈጠረው ሠላም ፊቱን ወደ ልማት ለማዞር ከፍተኛ ተነሳሽነት ላይ የሚገኘውን ዜጋ በዚህ ችግር ተጠልፎ በመንግሥት ላይ ቅሬታ እንዳያሳድር ፈጣን ምላሽ መስጠት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ይጠበቃል፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

በአገሪቱ እየተበራከተ የመጣውን የሥራ አጥነት ችግር ለማቃለል ታስቦ ወደሥራ የተገባበት የቴክኒክና ሙያ ስልጠና መርሐ ግብር በሚፈለገው ልክ ውጤት አለማምጣቱን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ለመሆኑ የቴክኒክና ሙያ ስልጠናው ለሥራ አጥነት ችግሩ በሚፈለገው ልክ አጋዥ አልሆነም ሲባል ምን ማለት ነው?

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚስቶች ማህበር ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሰኢድ ኑሩ እንደሚናገሩት፤ የአንድ አገር ህዝብ ለአገሩ የለውጥ ኃይል የመሆኑን ያክል ሸክምም የሚሆንበት አጋጣሚ አለ፡፡ ምክንያቱም ህዝቡ በተገቢው እውቀትና ክህሎት ተገንብቶና ባወቀው መስክ ተሰማርቶ ማምረትና አገልግሎት መስጠት ሲችል የልማት ኃይል ይሆናል፡፡ ይህ ካልሆነና የሰው ኃይሉ ከቁጥር ባለፈ የሙያና ክህሎት አቅም ፈጥሮ መሳተፍ ካልቻለ ግን ሸክም መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡
ዶክተር ሰኢድ፣ በዚህ ዙሪያ ያከናወኑትን ጥናት ዋቢ አድርገው እንደሚናገሩት፤ በኢትዮጵያ ደረጃም ዛሬ ላይ እስከ 100 ሚሊዮን የሚገመተው ህዝብ በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሰማርቶ የልማትና ዕድገቱ አጋዥ እንዲሆን በእውቀትና ክህሎት ሊገነባ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ለመፍጠርና በሁሉም መስክ ሥራ ላይ ሊሰማራ የሚችል የሰው ኃይል ለመፍጠር የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሰፊ ድርሻ አላቸው፡፡ ይህንን እንዲወጡ የሚያስችል የቴክኒክና ሙያ ትምህርትም በፖሊሲ ተቀርፆ ይገኛል፡፡ ሆኖም ከተደራሽነት ባለፈ ጥራት ላይ እየተሰራ ያለው ሥራ አነስተኛ በመሆኑ እነዚህ ተቋማት ሥራ ፈጣሪ ትውልድን ከመፍጠር አኳያ የሚፈለገው ደረጃ ላይ አልደረሱም፡፡
በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሻለ በሬቻም በዶክተር ሰኢድ ሃሳብ ይስማማሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በእውቀትና ክህሎት ታንጸው ወደሥራ የሚሰማሩ ዜጎችን የማፍራት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በዚህም ከ600 በላይ የመንግሥትና ከ800 በላይ የግል ኮሌጆች በመደበኛ መርሐ ግብር እስከ 200ሺ፣ በአጫጭር ስልጠና ደግሞ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰልጣኞችን በየዓመቱ እያሰለጠኑ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ከኢንዱስትሪው ተሳትፎ፣ ከአቅርቦትና ፍላጎት እንዲሁም በስልጠና ሂደት ላይ በሚያጋጥሙ ችግሮች እነዚህ ተቋማት በሚፈለገው ልክ ለሥራ ዕድል ፈጠራው አጋዥ መሆን አልቻሉም፡፡
እንደ አቶ ተሻለ ገለጻ፤ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ከኢንዱስትሪው ተለይተው የማይታዩ ቢሆንም፤ በስልጠናም ሆነ በምዘና የኢንዱስትሪው ተሳትፎ ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህም ሰልጣኞች አብዛኛውን ጊዜ በማሰልጠኛ ተቋማት እንዲያሳልፉ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ ተቋማቱ በተለመደው መንገድ ከማሰልጠን ባለፈ ገበያው የሚፈልገውን ባለሙያ ስለማያፈሩ ሰልጣኞች በገበያው እንዳይፈለጉ አድርጓቸዋል፡፡ ለአብነትም፣ በመደበኛው መርሐ ግብር ሰልጥነው ከወጡት ውስጥ 68 በመቶው፤ በአጫጭር መርሐ ግብሮች ሰልጥነው ከወጡት ደግሞ 73 በመቶዎቹ ብቻ ወደሥራ ይገባሉ፡፡ የሚሰጠው ስልጠና በተቀመጠው የ70/30 ስታንዳርድ መሰረት በተግባር ስለማይደገፍም ባለሙያዎች ጥራት ያለው ስልጠና ወስደውና አቅም ፈጥረው እንዳይወጡ፤ በራሳቸውም ተወዳዳሪና ሥራ ፈጣሪ እንዳይሆኑ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡
በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ የሙያ ደረጃ ምደባና ብቃት ምዘና ዳይሬክተር የሆኑት ወይዘሮ ንግስት መላኩ፣ የአቶ ተሻለን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሥራ ፈጠራ አጋዥነት ሚናቸው የሚለካው በሚያወጧቸው ሰልጣኞች ጥራትና በተሰማሩበት መስክ በሚያስመዘግቡት ውጤት ነው፡፡ ይህም ሰልጣኞች አንድም በመቀጠር፤ ሁለተኛም በራሳቸው በግልም ሆነ በጋራ ሥራ መፍጠር ሲችሉ፤ ቴክኖሎጂን በመቅዳትም ሆነ በመፍጠር የሚያመርቱትን ምርት በጥራት ሲያመርቱ፤ የሚሰጡትን አገልግሎትም በብቃት ሲያደርሱ የሚረጋገጥ ይሆናል፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ ተቋማቱ በሚፈለገው ልክ የሥራ ፈጠራው አካል ሆነዋል ማለት አይቻልም፡፡
ዶክተር ሰኢድ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ዛሬ ላይ በገጠርም ሆነ በከተማ የሥራ አጥነት ችግሩ እየሰፋ ይገኛል፡፡ በትምህርትና ሙያ ተቋማት የሚፈጠረውም የሰው ኃይል ገበያውን መሰረት ያደረገ አይደለም፡፡ ገበያውም እየሰለጠነ የሚወጣውን የሰው ኃይል መቀበል አልቻለም፡፡ ባለሙያዎችም ተቀጣሪ ብቻ ሳይሆን ሥራ ፈጣሪም መሆን የሚጠበቅባቸው ቢሆንም፤ አሁን ያለው ሁኔታ ተወዳዳሪና ከራስ አልፎ ለሌሎች የሥራ ዕድል ሊፈጥር የሚችል ቴክኖሎጂን ከማውጣትና የሥራ ዕድል ፈጣሪ ከመሆን አኳያ የሚፈለገውን ያክል አልሄዱም፡፡ ይህ ደግሞ ዘርፉ በሚፈለገው ልክ ብቁ የሆነ የሰው ኃይል ላለማፍራቱ ማሳያ ነው፡፡
የአገሪቱን የማምረቻ፣ የንግድና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በቴክኒክና በሙያ ብቃት ያለው የሰለጠነ የው ኃይል ቀጥሮ በማሰራት ብቁ ተወዳዳሪና ዘላቂነት ያለው ድርጅታዊ አቋም እንዲኖራቸው ለማስቻል፤ ወጣቱ የሥነልቦና ዝግጅት፣ የሥራ ዲስፕሊንና ችሎታ ያለው ብቁ ተቀጣሪና ሥራ ፈጣሪ እንዲሆን የሚያግዝ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ሥርዓት ለማደራጀት፤ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ፕሮግራም ብቃት ያለው የሰው ኃይል እንዲያዘጋጅ ሰልጣኞች ከመመረቃቸው በፊት በአምራችና አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ተሰማርተው የሥራ ልምምድ የሚያደርጉበት ሥርዓት ለመዘርጋት፤ ሲባል የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና አዋጅ ቁጥር ፫፻፺፩/፲፱፻፺፮ (391/1996) መደንገጉ ያታወቃል፡፡
ዶክተር ሰኢድ እንደሚናገሩት፤ ሰፊ ህዝብ ሲኖር ሰፊ የገበያ ዕድል ይኖራል፡፡ የተለያዩ የለውጥና የቴክኖሎጂ ሃሳብም ይመነጫል፡፡ ይህ እንዲሆን ግን የሰው ሀብቱ በዕውቀት የዳበረ፣ ጤናው የተጠበቀ፣ ከሱስ የነጻና በስነምግባር የታነጸ፣ ሰፊ የሥራ ዕድል አማራጭ ያለው ሊሆን ይገባል፡፡ እነዚህን ነገሮች ካሳካ ህዝብ ሀብት ነው፤ ካልሆነ ግን የሰው ሀብቱ ሸክም መሆኑ አይቀርም፡፡ አሁን ያለው የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ስልጠና ሂደትም በዚሁ ከቀጠለ፤ በየዓመቱ ከተቋማቱ የሚወጣው የሰው ኃይል ባለሙያ ሆኖ አገርን ከመደገፍ ይልቅ የአገር ሸክም የማይሆንበት ምክንያት አይኖርም፡፡

ዜና ትንታኔ
ወንድወሰን ሽመልስ

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።