Items filtered by date: Tuesday, 08 May 2018

ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ በሴቶች ማስመዝገብ ከቻለችበት እ.አ.አ የ1992 የስፔኑ ባርሴሎና ኦሎምፒክ ጀምሮ በአትላንታ፤ በሲድኒ፤ በአቴንስ ተሸጋግሮ 2008 ቤጂንግ ኦሎምፒክ ላይ መቋጫውን ባደረገው ለ16 ዓመታት በዘለቀው የዋና አሰልጣኝነት ዘመናቸው ኢትዮጵያውያንን በሃሴት የናጡ የአትሌቲክስ ድሎችን ተቀዳጅተዋል።አሰልጣኝ ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ።

ሰማይና ምድር ሳይላቀቅ ማለዳ ተነስተው ከአትሌቶች ጋር ደፋ ቀና የሚሉት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ መሐንዲሱ ሰው፤ የስታዲየም ትራክ፣ የሰንዳፋ ሜዳዎች፣ የእንጦጦ ጫካዎችና የኮተቤ ዙሪያ ተራሮች ያለመታከት የሥልጠና ሂደታቸው መቀመሪያ አድርገው ተጠቅመውባቸዋል።
በእርሳቸው የአሰልጣኝነት ክህሎት ተገርተው ወደ ስኬት ሰገነት የወጡ ከአህጉራዊ ውድድር እስከ ታላቁ ኦሎምፒክ ድረስ የወከሉ፤ ያኮሩ፤ በድል ስሜት ሃሴትን ያቀዳጁ የአሸናፊነት ምልክት የፅናት አብነት የሆኑ አትሌቶች ጀግኖችን ፈጥረዋል።
ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ጋር ለሦስት አስርት ዓመታት ደፋ ቀና ያሉት ሰው በስፖርቱ ዓለም ሥነምግባር የሚያስገኘውን ጠቀሜታ በማሳየት የኢትዮጵያን አትሌቲክስ መልካም ስም ገንብተዋል። የአሸብራቂ ድሎች ፈጣሪነት፤ ታታሪነት፤ ጠንካራ የአገር መውደድ ስሜት መለያ ባህሪያቸው የሆነው እኝህ ሰው አትሌቶች በተለይ አገርና ሕዝብ በማክበር የታነፁ እንዲሆኑ ያለመታከት ሰርተዋል። አትሌቶቻቸውን የሚያንፁት፤ የሚቀርፁትና የሚፈጥሩት በዚህ ትልቅ ዋጋ በሚሰጡት የአገር ክብር ዙሪያ ነው።
እርሳቸው ቢሆን በአሸናፊነት ሜዳሊያ በተንቆጠቆጠው የአሰልጣኝነት ሥራቸው የተደነቁ ከበርካታ አገራት የእንቅጠርህ ጥያቄ በተደጋጋሚ ቢቀርብላቸውም ለአገርና ወገናቸው ባላቸው ጥልቅ ፍቅር ምክንያት ጥያቄውን ወደ ጎን በመግፋት ሙሉ ዕድሜያቸውን አገራቸውን በማገልገል አሳልፈዋል።
እኚህ የአትሌቲክሱ ማዕዘን ወደዚህች ምድር የመጡት በ1942 ነበር። ትውልዳቸው በሰሜን ሸዋ ተጉለትና ቡልጋ ሲሆን ወላጆቻቸው በግብርና ሙያ የሚተዳደሩ ነበሩ፡፡ እንደ እነሱ ፍላጎት ቢሆን ኖሮ ዶክተር ወልደ መስቀል አሰልጣኝ ሳይሆን የቤተ ክህነት አገልጋይ ይሆኑም ነበር። ይሁንና የ11 ዓመት ታዳጊ ሳሉ ከእናታቸው ዘመዶች ጋር እየኖሩ የሚማሩበት አጋጣሚ በመፈጠሩ የትውልድ መንደራቸውን ተሰናብተው አዲስ አበባ ገቡ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ለመከታተል ከቻሉ በኋላ በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚካሄድ የስፖርት ውድድሮች ጠንካራ ተሳትፎ ከማድረጋቸውም በላይ በተለይ በእግር ኳስ ተጫዋችነት ይታወቁም ነበር፡፡ በወጣትነት ዘመናቸው ላይ ከእግር ኳስ ባሻገር በአጭርና መካከለኛ ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች የሚሳተፉ ምርጥ አትሌት የመሆን ፍላጎት አድሮባቸው በዚያው አቅጣጫ በትጋት ተሳትፏቸውን ቀጥለዋል፡፡
ዶክተር ወልደ መስቀል የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝተው ወደ ምሥራቅ አውሮፓዋ ሀንጋሪ ከማምራታቸው ከሳምንታት በፊት እ.አ.አ በ1964 አበበ ቢቂላና ማሞ ወልዴን የመሳሰሉ ኮከቦች በቶኪዮ ኦሎምፒክ ሲሳተፉ እርሳቸውም ለአትሌቲክስ ቡድኑ በተወዳዳሪነት ተመርጠው ነበር፡፡
ነገር ግን ትምህርት ይሻለኛል በማለት ውድድሩን በመተው ወደ ሀንጋሪ አምርተዋል፡፡ በሀንጋሪም ሁለት ጊዜያት ተመላልሰው 14 ዓመታትን በመቆየት በባዮሎጂ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ የዶክትሬት ዲግሪ ባለቤት ሆነዋል፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአካል ማጎልመሻ ትምህርት ባገኙባት ሀንጋሪ በዩኒቨርሲቲ ጨዋታዎች ኮሌጃቸውን ወክለው በ5 ሺ እና 10ሺ ሜትር ተወዳድረውም ነበር ፡፡
ወደ አገር ቤት ከተመለሱ በኋላ በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በ1962 ዓ.ም በስፖርት መምህርነት ሥራቸውን እየሰሩ በተጓዳኝ የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድንን በአካል ብቃት አሰልጣኝነት አገልግለዋል። የቅዱስ ጊዮርጊስን እግር ኳስ ክለብንም አሰልጥነዋል፡፡ በስፖርት ኮሚሽን ውስጥ በከፍተኛ ባለሙያነት ሰርተዋል፡፡ የአትሌቲክስ አሰልጣኝነትን የጀመሩት በኮተቤ ኮሌጅ አስተማሪ እያሉ በ70ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሲሆን በ1972 የሙኒክ ኦሎምፒክ በሚሳተፈው ቡድናችን ዋና አሰልጣኝ ለነበሩት ንጉሴ ሮባ ምክትል በመሆን ሰርተዋል፡፡
የአበበ ቢቂላ፤ የማሞ ወልዴ፤ የምሩፅ ይፍጠርና ሌሎች የቀድሞ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ጀግኖች ፈጣሪ የሆኑት አሰልጣኝ ንጉሴ ሮባ በ1984 ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ተክትሎም ዶክተር ወልደመስቀል የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ስፖርት በዋና አሰልጣኝነት በይፋ ተቀላቀሉ።
ዶክተር ወልደመስቀል የኢትዮጵያን አትሌቲክስ የቅብብሎሽ አደራ ከንጉሴ ሮባ መቀበል ብቻም ሳይሆን በአገሪቱ የስፖርት ታሪክ እጅግ ስኬታማ አሰልጣኝ አስብሎ ያስፈረጃቸውን፤ በኢትዮጵያውያን ተቀናቃኞች ዘንድ ደግሞ ግርማ ሞገስ ያላበሳቸውን ስኬት ማስመዝገብ የጀመሩት ሥራቸውን በጀመሩ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ነው።
በተለይ እ.አ.አ በ1990ዎቹ ኃይሌ ገብረሥላሴና ደራርቱ ቱሉን ፊታውራሪ ያደረገው የኢትዮጵያውያን ሳተና ሯጮች ዓለምን በድል የመውረር አብዮት በጌጤ ዋሚ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ በአሽናፊነት ተቀባብሎ በጥሩነሽና እጅጋየሁ ዲባባ በመሠረት ደፋርና በመሰለች መልካሙ እንዲሁም ገለቴ ቡርቃ ተተከቶ ሲቀጥል ድላማው የኮስትሬ ልጅ የሥልጠናው አሸጋጋሪ ህያው መስመር ሆኖ አገልግሏል።
ኢትዮጵያ በሁሉም ኦሎምፒክ ተሳትፎዋ ካገኘቻቸው ሜዳልያዎች 28ቱ የተገኙት በእኝሁ ስመ ጥር አሰልጣኝ ሲሆን፣ ሰውየው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድንን እያሰለጠኑ በተሳተፉባቸው አምስት ኦሎምፒኮች ላይ 11 የወርቅ ሜዳሊያዎችን አስገኝተዋል፡፡

የዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ ሐውልት፤


በእርግጥም እውቀት፣ ልምድ እና ብቃትን አጣምረው መያዝ የቻሉት አሰልጣኝ ዶክተር ወልደመስቀል ለኢትዮጵያውያን አትሌቶችና አትሌቲክስ ልዕልና ዋነኛ ምሰሶ ናቸው። ፍልቅልቋ ደራርቱ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ በመሆን ለአፍሪካም ሆነ ለአገሯ የመጀመሪያዋ ሴት አትሌት የሆነችበትን ታሪክ ስታስመዘግብ ትልቁን የቤት ሥራ የሰሩት እኒህ ለአገራቸው ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ባለውለታ የሆኑት ሰው ናቸው።
አትሌት ደራርቱም ብትሆን ከባርሴሎና ተነስታ ወደ ዓለም አቀፍ ኮከብነት በኋላም የኢትዮጵያ አትሌቲስክ ምልክት ለመሆን የበቃቸው በዶክተር የአሰልጣኝነት ቀመር በመታገዝ መሆኑን ሁሌም ትገልፃለች። ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ በ1996 አትላንታ ላይ ታሪክ ሲሰራ እንዲሁም በተደጋጋሚ የዓለም ክብረ ወሰኖችን ሲሰባብር ብሎም የሩጫ ብቃትና ችሎታውን የተመለከቱም «ይህማ ከሌላ ፕላኔት የመጣ ነው እስኪባል ድረስ» ሲያሞካሹት በተለይ በኦሎምፒኩ የዶክተር ወልደመስቀል ሚና ጉልህ ድርሻ እንደነበረው ከመግለፅ አይቆጠብም።
ይህ የዶክተር ወልደመስቀል ጥልቅ የስፖርት ፍቅርና የአሰልጣኝነት ክህሎት ብሎም አስደናቂ ድሎች የታጀበ የሦስት አስርት ዓመታት የአትሌቲክስ ጉዞም አገር ውስጥን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ተችሮታል።
በተለይም ዓለምአቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን አይ ኤኤ ኤፍ በ2006 የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝ ብሎ መርጧቸዋል። እ.አ.አ በ2011 የአፍሪካ ኮከብ አሰልጣኝ ተብለው በሞሮኮ ማራካሽ ለሽልማት በቅተዋል። ከሦስት ዓመት በፊት ደግሞ በአገር ውስጥ የበጎ ሰው ሽልማትን በስፖርት ዘርፍ አሸንፈዋል።
ይህ ከአገር ውስጥ እስከ ውጪ፤ ከተወዳዳሪነት እስከ አሰልጣኝነት፤ ከተማሪነት እስከ አስተማሪነት ከትንሽ ውድድር እስክ ኦሎምፒክ የዘለቀ የዶክተር ወልደመስቀል ስኬታማ የአትሌቲክስና የግል ሕይወት ግን ከሁለት ዓመት በፊት ለመቆም ተገዷል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ መሐንዲስና ድላማው አሰልጣኝ 2008 ዓ.ም ግንቦት ወር ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ድል አድራጊው አሰልጣኝ ይህን ዓለም ቢሰናበቱም ሥራቸው ግን ሁሌም ህያው ሆኖ ይኖራል።
አረንጓዴው ጎርፍ የሚለውን መጠሪያ ለኢትዮጵያ ካሰጡት አንዱና ግንባር ቀደሙ ነው። የሞስኮ ኦሎምፒክ ሲነሳ ቀድሞ የሚታወሰውና የሚወሳው የእርሱ ስም ነው። በዚህ መድረክ በድል ቁርጠኝነት የተሞላበት አሯሯጡ የመላው ዓለም ምናብ ስንግ አድርጎ መያዙም አይረሳም። በኦሎምፒኩ በሁለቱም ርቀቶች በ 5 እና 10 ሺ ሜትር ለተቀናቃኞቹ ዕድል ሳይሰጥ አፈትልኮ በመውጣት ያሸነፈበት ክስትት «ይፍጠር ዘ ሺፍተር፤ ማርሽ ቀያሪው» የሚል ቅፅል ስምን አሰጥቶታል። ከሞስኮ ኦሎምፒክ ድል በኋላ ጥንታዊ ኦሎምፒክ በተመሰረተባት ግሪክ ለኦሊምፒያዊ ሽልማት ከተመረጡ አምስት አትሌቶች ቀዳሚ ሆኖ የኦሎምፒክ ሎሬት አክሊልን ከርዕሰ ብሔሩ ተቀብሏል። ጀግናው አትሌት ምሩፅ ይፍጠር።
በሞስኮ ኦሎምፒክ ለሦስተኛ ጊዜ ድሉን ለማጣጣም ቆርጦ የነበረው ፊንላንዳዊው ላሲ ቬረን በሞስኮ አየሩ ጥሩ ከሆነ እንደሚያሽንፍ መናገሩን ተከትሎ ምሩጽ በሰጠው የአፀፋ ምላሽ «ሃሩርም ይሁን በረዶ እኔ ከማሸነፍ የሚገታኝ አንዳች ኃይል የለም» ማለቱም ልበ ሙሉነቱን ያሳየበት ንግግር ሆኖ አትሌቱ ሁሌም ይታወሳል።
የጀግናው አትሌት የትውልድ ቦታ መቼት በቀድሞው አጠራር በትግራይ ክፍለ አገር አዲግራት አውራጃ በዛላንበሳ ወረዳ እምበይቶ አዲ ቁልቋ ቀበሌ በ1936 ዓ.ም ነው። የዚህ የአትሌቲኩ ዓለም ታሪክ መቼም የማይረሳው አስደናቂ ድል መነሾ እጅጉን አስገራሚ ነው። መስከረም በ1961 ዓ.ም አበበ ቢቂላና ማሞ ወልዴን የያዘው የኢትዮጵያ ተሳታፊ አትሌቶች ቡድን የመጨረሻ ጉዟቸውን ወደ ሜክሲኮ ኦሎምፒክ ከማድረጉ በፊት ለልምምድ ያረፈው አስመራ ከተማ ንግስተ ሰባ ስታዲም ነበር። ይህ በንግስተ ሰባ ስታዲም የሚካሄደው የብሔራዊ አትሌቶች ልምምድ ታዲያ ለአንድ ሰው ከምንም በላይ ወሳኝ የሕይወት አጋጣሚና ከአትሌቲክስ ሕይወቱ ገናና ስሙ ዋነኛ መነሾ ክስትት ሆነ።
ምንም እንኳን ምሩፅ በልምምድ ውድድሩ ተሳትፎ ከአትሌቶቹ መጨረሻ ቢወጣም አሯሯጡንና አቅሙን ያስተዋለው ጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ ግን በአየር ኃይል ስፖርት መምሪያ እንዲያዝና ልምምድ እንዲያደርግ አደረገው። «ንብ» የሚባለውን የአየር ኃይል ስፖርት ክለብን እየወከለ በብሔራዊ ሻምፒዮናና በጦር ኃይሎች ውድድር ውጤታማ መሆን ጀመረ። የምሩፅ የሩጫ ብቃትና ውጤታማነትም ባህር ለመሻገር ብዙ ዓመታትን መጠበቅ ግድ አላለውም።
በዓለም አቀፍ መድረክ የምሩፁና የወርቅ ትውውቅ የጀመረው በ1963 ዓ.ም ነው። በዚህ ዓመት በአሜሪካ በተካሄደው የአፍሮ አሜሪካን ውድድር በ 10 ሺ ሜትር ወርቅ፤ በ 5 ሺ ሜትር ደግሞ የብር ሜዳሊያ አግኝቷል።
ምሩፅና የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ የተገናኙት ደግሞ በ972 ዓ.ም ሲሆን ሁነቱ የ22ተኛ የሞስኮ ኦሎምፒያድ ነው። ምሩፅ በዚህ መድረክ በሁለቱም ርቀቶች ወርቁን ማጥለቅ ችሏል። ከሞስኮው ወርቃማ ድሉ በተጓዳኝም በ1969 እና 1971ዓ.ም በተካሄዱት የዓለም አትሌቲክስ ዋንጫዎች አፍሪካን በመወከል አራት የወርቅ ሜዳሊያ በማምጣት የአገሩን ስም ከፍ አድርጎ አስጠርቷል።
1971ዓ.ም ለምሩፅ ከምንም በላይ ልዩና ወርቃማው ዓመት ነው። የድል ምልከት የሆነው አትሌት በዓለም የአትሌቲክስ ስፖርት መድረክ እጅጉን የገነነውና ታላቅ ክብርን በተቀዳጀበት በዚህ ዓመት ሲሆን፣ በቼኮዝሎቫኪያ በተዘጋጀው የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ «የኮከቦች ኮከብ» በሚል የወርቅ ጫማ ተሸልሟል።
ምሩፅ የሩጫ ሕይወቱን በ 1 ሺ 500 ሜትር ቢጀምርም በ 5 እና 10 ሺ ሜትር ውድድሮች መደበኛ ውድድሮች አሸናፊነትን ደጋግሞ አሳይቷል። ማርሽ ቀያሪው ሰው ከመም ሩጫ የድል ታሪኩ በተጓዳኝ በጎዳና ላይ ሩጫዎችም ተደጋጋሚ ድሎችን አስመዝገቧል። በተለይ በተከታታይ ዓመታት ድል የተጎናፀፈበት የፖርቶ ሪኮ ግማሽ ማራቶን ውድድር ለዓለም ክብረ ወሰን አብቅቶታል። በተለይ ጥር 29 ቀን 1969 ዓ.ም የተካሄደውን ውድድር ሲያሽንፍ የገባበት 1 ሰዓት ከ 02 ደቂቃ ከ 57 ሴኮንድ የዓለም ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝገቧል። እነዚህን ለአብነት እንሳን እንጂ ማርሽ ቀያሪው ማርሽ ቀይሮ ያላሸነፈባቸው ውድድሮች ጥቂትና አሉ ከሚባል የሉም ለመባል የቀረቡ ናቸው።
የዚህ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስፖርት የድል ምልከት የአትሌቲክስ ሕይወት ፍፃሜ ግን እጅጉን አሳዛኝ ነበር። «ይፍጠር ዘ ሺፍተር» የአልጋ ቁራኛ ሆኖ የተናገረው ንግግር ግን ሁሌም ለአገርና ለሕዝብ ክብርና ፍቅር እንዳለው ያስመሰከረበት ነበር።
ጀግናው አትሌት በወቅቱ ከህመሙ እንዲያገግም እጅጉን ውድ እና በገንዘብ የማይተመኑ ሽልማቶቹ በጨረታ ተሽጠው ለህክምና እንዲውሉ ሲጠየቅ «ሽልማቶቼ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ናቸው ለሽያጭ አይታሰቡም» ሲል ነበር መልስ የሰጠው። ሜዳሊያዎቹን ከመሸጥ ይልቅ ለአገርና ሕዝብ ክብር ማስታወሻነት በመወሰኑም ሕይወቱን ማትረፍ ሳይችል ቀርቷል።
ዛሬ የእነዚህን ሁለት የኢትዮጵያ አትሌቲስክ የድል ምልክቶች ገድል በወፍ በረር ማውሳታችን ያለምክንያት አይደለም። ባሳለፍነው እሁድ የኢፌዴሬ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከጀግናው ምሩፅ ይፍጠር ቤተሰብ ጋር በመተባበር ለሁለቱም የድል ምልክቶች ክብር አጽማቸው ባረፈበት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን የቆሙትን ሐውልቶች ማስመረቃቸውን ዋቢ በማድረግ ነው።
የጀግኖቹን ታሪክ መዘከርን ዓላማው ያደረገው የሐውልት ምርቃ ሥነ ሥርዓት ያቀደውን በእጅጉ አሳከቷል። አትሌቶች የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም የኮከቦቹ እና የስፖርቱ አድናቂዎች ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ በርካታ ወገኖች የኢትዮጵያን አትሌቲክስ የድል የኩራትና የክብር ምልክቶች ለማክበር በተዘጋጀው የሐውልት ምርቃት ፕሮግራም ላይ ታድመዋል። ለጀግኖቻቸውም ክብር ሰጥተዋል። የአትሌቱቹ ቤተሰቦችም ስለተደረገው ሁሉ ደስተኛ ሆነው ታይተዋል።
በምርቃ ሥነሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኢፌዴሬ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ርስቱ ይርዳው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ፤ የኢትዮጵያ አትሌቲስክ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ፤ ሁለቱ ኮከቦች በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ስፖርት ታሪክ ባስመዘገቧቸው የላቁ ውጤቶችና ጉልህ አስተዋፅኦዎች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ መሆናቸውን አውስተዋል። በአገር ፍቅርና ወኔ የፈፀሙት የአሸፊነት ገድል ጊዜ የማይሽረው የማይደበዝዝና ዘላለማዊ በመሆኑም ሁሌም እንዲታወሱ የሚያደርግ ሲሉም ተደምጠዋል።
በተለይ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ርስቱ ይርዳው፤ አገሪቱን በዓለም አደባባይ ማስጠራት የቻሉ ፈርጦችና ጀግኖች በሕይወት እያሉ ከጎናቸው በመቆም ከመደገፍ ባሻገር ወደ ማይቀረው የፈጣሪ ጥሪ በሚሄዱበት ወቅትም መታሰቢያ እንዲኖራቸው በማድረግ ትውልድ እየዘከራቸው እየተማረባቸው እንዲዘልቅ ማድረግ እጅግ እስፈላጊ መሆኑን ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያን አትሌቲክስ የድል የኩራትና የክብር ምልክት የሆኑ አትሌቶች «ቋሚ የስማቸው ማስታወሻና መጠሪያ ከሁሉ በላይ የፈፀሙት ህያው ተግባራቸው ነው፤ ይሁንና አፅማቸው ባረፈበት ቦታ የድላቸውን ውሎ የሚገልጽ ሐውልት ማቆም ተገቢና ለትውልድ የሚኖረው የአስተማሪነት ፋይዳ እጅጉን ከፍተኛ መሆኑም ሊታወቅ ይገባልም» ነው ያሉት።
በእርግጥ አገሪቱ የኩራትና የክብር ምንጮቿን አክብራ መሸኘቷ የሚታወስ ሲሆን በጋራ ከትናንት በስቲያ የተደረገው የጀግኖቹ የሐውልት ምርቃት ደግሞ በብዙዎች ዘንድ አድናቆት ተችሮታል። በሌሎችም ስፖርተኞች ዘንድ እንዲደገም የጠየቁም በርካታ ሆነዋል።

ታምራት ተስፋዬ

 

Published in ስፖርት
Tuesday, 08 May 2018 16:54

«ቲፕ» ባጋጣሚ

በሀገራችን የካፍቴሪያና የሬስቶራንት አገልግሎት በሚሠጡ ቤቶች ውስጥ ደንበኞች ሲገለገሉ ለተደረገላቸው መልካም መስተንግዶ ጉርሻ ወይም ቲፕ ለአስተናጋጆች የመሰጠቱ ባህል ተለምዷል፡፡ የጉርሻው መጠንም እንደ ደንበኛው አቅምና ፍላጎት ይወሰናል፡፡ በዚህ ሂደት አንዳንዱ ለታይታ በሚል ኪሱን አራግፎ ገንዘቡን ሲያስረክብ ሌላው ጥቂት ሳንቲም ብቻ ጣል አድርጎ ይወጣል፡፡ ያው ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባለም አይደል የሚባለው፡፡ ሌላው ደግሞ ለተደረገለት መስተንግዶ አመሰግናለሁ ወይም ፈጣሪ ይስጥልኝ ሳይል አንድም ሳንቲም ሳይሰጥ ውልቅ ብሎ ይወጣል፡፡ ለነገሩ መብቱ ነው!
የቲፕን ነገር ቲፕ ያነሳዋልና ከሰሞኑ ኦዲቲ ሴንትራል የተሰኘው የመዝናኛ ድረገፅ ያወጣው መረጃ ቲፕ እንደዚህም ይሰጣል እንዴ? የሚያሰኝ ነው፡፡
ኦሌስጃ ሼምጃኮዋ የተሰኘችው የ37 ዓመቷ ሩሲያዊት ወይዘሮና ልጇ ቡናና ኬክ ቢያምራቸው ዙሪክ ውስጥ በሚገኝ አንድ ካፊቴሪያ ጎራ ይላሉ፡፡ ቡናና ኬካቸውንም ያጣጥማሉ፡፡ ጊዜው ሂሳብ የመክፈያ በመሆኑ ወይዘሮዋ የክሬዲት ካርዷን በማውጣት ክፍያ ትፈፅማለች፡፡ ይሁን እንጂ የክሬዲት ካርዷን የምስጢር ቁጥር በማስገባት ፈንታ የቲፕ መስጫ የምስጢር ቁጥሩን በመንካቷ 23 የስዊዝ ፍራክ መክፈል ሲገባት 7 ሺ 709 ፍራንክ ለአንድ ቡናና ቁራሽ ኬክ ከፍላ ታርፈዋለች፡፡ በሚገርም ሁኔታ ወይዘሮዋ መሞኘቷን ያወቀችውም ከፍያውን ከፈፀመች ከአንድ ወር በኋላ የክፍያ ደረሰኝ በመጣላት ጊዜ መሆኑ ነው፡፡
ወይዘሮዋ እንደ ምንም ድንጋጤዋን ተቆጣጥራ ክሬዲት ካርድ ከወሰደችበት ኩባንያ በመሄድ በስህተት ለካፍቴሪያው ክፍያ እንደፈፀመችና ያወጣችውንም ገንዘብ እንዲመልሱላት ብትማፀንም ምንም ማድረግ እንደማይችሉና ይልቁንም የእርሷ ጉዳይ የመጭበርበር እንዳልሆነ አስረግጠው ይነግሯታል፡፡ ወደ ፖሊስ በመሄድም ተዘረፍኩ ብላ አቤት ብትልም ፖሊሶቹም በተመሳሳይ ጉዳይሽ በምንም ዓይነት መልኩ ከወንጀል ጋር አይገናኝም ሲሉ ኮስተር ብለው ይመልሱላታል፡፡
ምንም አማራጭ እንደሌላት የተረዳችው ይህችው ሩሲያዊት ወይዘሮ በቀጥታ የካፍቴሪያውን ባለቤት ለማነጋገር ትወስናለች፡፡ ወደዚያም በማምራት ገንዘቡን በቲፕ መልክ ለመስጠት እንዳልፈለገችና መሳሳቷን ታስረዳለች፡፡ የካፍቴሪያው ባለቤት ወይዘሮዋ በቲፕ መልክ በስህተት ያወጣችውን ወጪ በወሩ መጨረሻ ላይ እንደሚመለስላት ሲገልፅላት እፎይታ ታገኛለች፡፡ ይሁን እንጂ ገንዘቡን የመስጫ የመጨረሻዎቹ ቀናት እየተቃረቡ ሲመጡ የካፌው ባለቤት የወይዘሮዋን የስልክ ጥሪና የኢሜል መልዕክት ሳይመልስ ይቀራል፡፡ ግንኙነታቸውም ሙሉ በሙሉ ይቋረጣል፡፡
በዚህ ነገር ዳግም የተደናገጠችው የ37 ዓመቷ ወይዘሮ የካፍቴሪያው ባለቤት በኪሳራ ምክንያት ካፌውን እንደዘጋውም በመጨረሻ ታረጋግጣለች፡፡ በዚህ ወቅትም ገንዘቧን በምንም ተአምር ልታገኝ እንደማትችልም ትደመድማለች፡፡
«የካፌው ባለቤት እንዴት ገንዘቡን ሊመልስልኝ እንደሚችል አላውቅም? ምን ማድረግ እንዳለበኝም ግራ ገብቶኛል? ስትል ስዊዝ ኒውስፔፐር ብሊክ ለተኘው የመገናኛ ብዙኃን ገልፃለች፡፡ ሠራ አጧ ወይዘሮ ገንዘቡን ባታጣ ኖሮ ለተወሰኑ ወራት በፈረንሳይ ዘና ልትል ሀሳቡ እንደነበራት ገልፃ፣ አጋጣሚው ህልሟን ቅዠት አድርጎባታል ሲል ዘገባው አትቷል፡፡

 

በካሮት ሱስ የወደቁት ካንጋሮዎች

 

በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ታሪክ ውስጥ ቀይ ቀበሮና ዋልያ ብርቅዬ መሆናቸው ሲጠቀስ፤ በአውስትራሊያ ደግሞ በዚህ መልኩ ስማቸው የሚነሳውና የበርካታ ቱሪስቶች ወደ አካባቢው መሄድ ምክንያት የሚሆኑት ካናጋሮዎች ናቸው፡፡
ከአውስትራሊያ ርዕሰ ከተማ ሲድኒ በባቡር የሁለት ሰዓት ጉዞ ከሚፈጀው የማኩሪን ሐይቅ አካባቢ ካንጋሮን ለመጎብኘት የሚመጡ በርካታ ቱሪስቶች ማስጠንቀቂያዎችን በመተላለፍ ለካንጋ ሮዎች ካሮት በመመገብ በቅርበት ለማየት ዕድል ቢፈጠርላቸውም ጥቃትም እየደረሰባቸው ነው ሲል ከሰሞኑ ሮይተርስ ያወጣው ዘገባ ያስረዳል፡፡
እንደዘገባው ከሆነ በየሳምንቱ በሺህ የሚቆጠሩ ቱሪስቶች ከአንድ የአእምሮ ህመምተኞች ሆስፒታል አቅራቢያ ወደሚገኝ ሳራማ ሜዳ ይተማሉ፡፡ ወደዚህ ቦታ የሚመጡበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ካንጋ ሮዎቹ ሰው ስለሚቀርቡና ፎቶ ለመነሳትም ዕድል ስለሚሰጡ መሆኑ ተገልጿል፡፡


በቅድሚያ ቱሪስቶቹ በእጃቸው ካሮት በመያዝ ይቀርቧቸዋል፡፡ ካንጋሮዎቹ ካሮቱን ለመብላት ስለሚጠጓቸው ከአውስትራሊያውያን ብርቅዬና የሀገሪቷ አርማ ከሆኑት ካንጋሮዎች ጋር የፈለጉትን ያህል ፎቶዎችን ይነሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ ይላል ዘገባው ከዚህ ጎን ለጎን ቱሪስቶቹ በእንስሳቱ ጥቃት እየደረሰባቸው ይገኛል፡፡
በፌስ ቡክ የማህበራዊ ድረ ገጽ ከተለቀቁ ፎቶዎች ውስጥም አንድ ቱሪስት በካንጋሮ ጠንካራ እግሮች ሲመታ ሌላዋ ደግሞ በደረሰባት ጥቃት ፊቷ ተሞነጫጭሮ እንዲሁም ሆዱ አካባቢ የቆሰለ ቱሪስት ፎቶዎች ታይቷል ይላል ዘገባው፡፡
«ካንጋሮዎች በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነው አንዳንዴ ቁጡ ሊሆኑ ቢችሉም ከ 90 በመቶ በላይ በካንጋራዎቹ ጥቃት የደረሰባቸው እነዚሁ ካሮት የሚመጉባቸው ቱሪስቶች ናቸው» ሲል ሼን ሊዊስ የተሰኘው የፓርኩ ቱሪስቶች አስጎብኚ ለሮይተርስ ገልጿል፡፡ ተመሳሳይ ጥቃት በአዳዲስ ቱሪስቶች ላይ እንዳይደርስም ጉዳት የደረሰባቸውን ጎብኚዎች ፎቶ እንደሚያሳይም አስጎብኚው ገልጿል፡፡
በሲድኒ ታሮንጋ እንስሳት ማቆያ የምግብ ባለሞያ የሆኑት ሚሼል ሾው፤ ካንጋሮዎች ከፍተኛ የስኳር መጠን ያለውን ካሮት ሊወዱ ቢችሉም ለእነሱ ግን አደገኛ ነው ፡፡ «ሰዎች ካሮት ይዘው ወደካንጋሮዎቹ ሲጠጉ ስኳር ያለውን ካሮት ለመመገብ ስለሚጓጉ ቁጡ ይሆናሉ» ሲሉም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የካንጋሮ ተፈጥሯዊ ምግብ በአብዛኛው ሳር መሆኑን የተጠቀሱት የምግብ ባለሞያው፤ በካሮት ውስጥ የሚገኘው ስኳር ሌሎች ንጥረ ነገሮች በቀላሉ በሰውነታቸው ውስጥ እንዳይገቡ ስለሚያደርግ ቀስ በቀስ በማዳከም ሊገድላቸው ይችላል፡፡
ለማህበራዊ ድረገጽ ምስጋና ይግባውና ይህ መረጃ ብዙዎች ዘንድ በመድረሱ አሁን የሞሪሴት ሆስፒታል የሚገኝበትን ቦታ 2ሺ የሚጠጉ ቱሪስቶች በየሳምንቱ እየጎበኙት ይገኛሉ ሲል ዘገባው ገልጿል፡፡
የአውስትራሊያ ፖለቲከኛ ግሬግ ፒፐር በበኩላቸው «ካንጋሮዎቹ ምንም እንኳን በቱሪስቶች ላይ ጥቃት ቢያደርሱም ቀደመው የዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን ትኩረት ስበዋል፤ እስካሁን ምንም ነገር አለመደረጉም ረፍዷል» ሲሉ ገልጸዋል፡፡ «ልናደርግ የምንችለው ነገር ቢኖር ለሰዎች ስለአደጋው ትምህርት መስጠትና ለቱሪስቶች ደህንነትና ለሆስፒታሉ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን የካንጋሮዎችንም ደህንነት ለመጠበቅ ሁኔታውን ለመቆጣጠር የሚያስችል መንገድ መፈለግ ነው» ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

Published in መዝናኛ

ከ2007 እስከ 2012 ዓ.ም ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የኢፌዴሪ የኤች አይቪ ኤድስ ስትራቴጂክ እቅድ፤ ተጽእኖ ፈጣሪና ኤች አይቪን መከላከል ላይ ያተኮረ ፕሮግራም ተግባራዊ ማድረግ ፣ የኤች አይቪ የምርመራና የምክር አገልግሎትን ማስፋት፣ ከእናት ወደ ልጅ ኤች አይቪ እንዳይተላለፍ ማቆምና ጥራቱን የጠበቀና ዘለቄታዊ የኤች አይ ቪ ህክምና መስጠት የሚሉ አራት መሰረታዊ ስትራቴጂካዊ አላማዎችን በመያዝ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ስትራቴጂክ እቅዱ ኤች አይቪ ኤድስን እ.ኤ.አ በ2030 የማቆም ራእይ የሰነቀና ከ70ሺ እስከ 80ሺ የሚሆኑ ሰዎች አዲስ በኤች አይቪ እንዳይያዙ መከላከልና ከ500 እስከ 550ሺ የሚሆኑትን ደግሞ በኤች አይቪ እንዳይያዙ የማድረግ ግብ ያነገበ ነው፡፡
የዚህ ስትራቴጂክ እቅድ የትግበራ ዘመን አጋማሽ ተደርሷል፡፡ከዚህ ጋር ተያይዞ ሰሞኑን ትግበራውን ልምድ ባላቸው ከተለያዩ ሀገራትና አለም አቀፍ ተቋማት በተውጣጡ ባለሙያዎች በመገምገም እቅዱን ለመከለስ አስፈላጊ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል፡፡ ግምገማው በሰነዶች ትንተናና በመስክ ጉብኝት እንደሚከናወንም ሰሞኑን ተጠቁሟል፡፡
የኢፌዴሪ ኤች አይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ፅህፈት ቤት ዳይሬክተር ዶክተር ሻሎ ዳባ እንደሚገልፁት፤ግምገማው የአምስት አመቱ የኤች አይቪ ስትራቴጂክ እቅድ ትግበራ የሁለት አመት ተኩል አፈፃፀም ምን እንደሚ መስልና ጠንካራና ደካማ ጎኖችን ለመለየት ያስችላል፡፡ በቀጣይም የትኩረት አቅጣጫዎቹ ምን መሆን እንዳለባቸው ለማወቅም ይረዳል፡፡ ግምገማው የእቅድ ክለሳ ለማድረግ የሚረዳ ሲሆን፣ ተአማኒነት እንዲኖረውም ከውጪ በመጡ ባለሙጭያዎች እንዲካሄድ ይደረጋል፡፡
ከውጭ ለኤች አይቪ ኤድስ መከላከል ስራ የሚገኘው የገንዘብ ድጋፍ እየቀነሰ መጥቷል ያሉት አቶ ሻሎ፣ የኤች አይቪ ኤድስ መድሀኒት ከግሎባል ፈንድ ለማግኘትና ፕሮፖዛል ለማቅረብ ተአማኒነት ያለው መረጃ እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ፡፡ይህ ገለልተኛ የሆነ አካል ሃላፊነቱን በደንብ ከተወጣ ክፍተቶችን መጠቆም የሚያስችል መረጃ ለማግኘት ይረዳል፡፡ ባለው ሀብት ውጤታማ ለመሆንና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገ ብም ከፍተኛ ክፍተት ባለበት ቦታ ላይ አትኩሮ ለመስራት ይጠቅማል፡፡ አለም አቀፋዊ ፕሮፖዛሎ ችንም በማዘጋጀት የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘትም ያስችላል ብለዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ ለክለሳ የሚያስፈልጉ የግምገማ የአፈፃፀም ሪፖርቶችን እንዲሁም በየክልሉ በመሄድ በተጨባጭ መሬት ላይ ያለውን በመመልከት የሚካሄድ ይሆናል፡፡ግምገማውን የሚያካሂዱት ባለሙያዎች ያለውን ክፍተት በደንብ ሊለዩ የሚችሉ፣ ሰፊ ልምድና ተሞክሮ ያላቸው ከዩ ኤን ኤድስ፣ ከዩ ኤስ አይ ዲ፣ ሲ ዲ ሲ፣ ዩ ኤን ኤፍ ፒ ኤን የተውጣጡ ናቸው፡፡ በአጠቃላይም 29 የሚጠጉ ባለሙያዎች በግም ገማው ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ ከአፍሪካ ሀገሮች የተውጣጡ ገምጋሚዎችም በግምገማው ይሳተ ፋሉ፡፡ በሂደቱ የሀገር ውስጥ ባለሙያዎችም የሚሳተፉ ሲሆን፣ ባለሙያዎቹ ከውጭዎቹ ባለሙ ያዎች ተሞክሮ እንደሚቀስሙም ይጠበቃል፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከበደ ወርቁ እንደሚገልፁት፤ የኤች አይቪ ኤድስ ስትራቴጂክ እቅድ ዘመን አጋማሽ አፈፃፀምን ለመገምገም ያስፈለገበት ምክንያት እስካሁን ያለውን አፈጻጸም መለስ ብሎ ለመቃኝት ነው፡፡ በግምገ ማው ሂደት በርካታ የውጭ ሃገር ባለሙያዎች መሳተፋቸው ግምገማው በገለልተኛ ወገን እንዲካሄድ የሚያስችል በመሆኑም የብሄራዊ ኤች አይቪ ኤድስ ፕሮግራምን ለማጠናከር ይረዳል፡፡ በክልልም ደረጃ የሚስተዋሉ ጠንካራ ጎኖችን ውደ ሌሎች ለማስፋት የሚያስችል ምክረ ሃሳብም ይገኝበታል፡፡ በአጠቃላይም የኤች አይቪ ኤድስ መከላከል ስራው የት ደረጃ ላይ እንዳለ ለማወቅ ይረዳል፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ፤ ግምገማው አለም አቀፉ ማህበረሰብ ኤች አይቪን ለመከ ላከልና መቆጣጠር ብሎም በ2030 ወረርሸኙን ለማቆም በሚደረገው ዘመቻ ሃገሪቱ የደረሰችበትን ደረጃ ለመገምገምና ክፍተቶችን ለመሙላትና በጥንካሬ ያሉትንም ለማስቀጠል ያግዛል፡፡
ባለፉት ሁለት አመታት ኤች አይቪ ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማስፋት ረገድ የተመዘገቡ ጠንካራ ስራዎች መኖራቸውን የሚጠቅሱት ሚኒስትሩ፤ እንደ ቀድሞው የማህበረሰብ ንቅናቄዎች በአግባቡ እየተካሄዱ ስለመሆናቸውም በግምገማው ሂደት መፈተሸ ያስፈልጋል፡፡
በኢትዮጵያ አለም አቀፉ የጤና ድርጅት የኤች አይቪ ኤድስ መከላከል የጥናት ፣ቁጥጥርና ግምገማ ባለሙያ ወይዘሮ እሌኒ ስዩም እንደሚሉት፤ የኤች አይቪ ኤድስ የመከላከል ፕሮግራም በሃገሪቱ ጠንካራ ከሚባሉ ፕሮግራሞች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ባለፉት አስር አመታት በኤች አይቪ ኤድስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር 80 በመቶ ቀንሷል፡፡ በኤች አይቪ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም እንዲሁ 80 በመቶ ቀንሷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም 436 ሺ የሚሆኑ ሰዎች የፀረ ኤች አይቪ መድሃኒቱን ይወስዳሉ፡፡
የኤች አይቪ ፕሮግራም በጥናትና በመረጃ ላይ ተመስርቶ ይመራ እንደነበር በመጥቀስም፣ ከዚህ አንፃር ትላልቅ ጥናቶችም በሃገር ደረጃ መሰራታቸውንም ባለሙያዋ ያመለክታሉ፡፡ የአሁኑ ግምገማ ዋነኛ መነሻም የዲሞግራፊክ ሄልዝ ሰርቬይ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
እንደ ወይዘሮ እሌኒ ማብራሪያ፤በአለም አቀፍ ደረጃ የአለም ጤና ድርጅት የሚያወጣው መረጃ የበሽታው ስርጭት መጠን እየቀነሰ መጥቷል፤ይሁን እንጂ ይህን ዘላቂ ለማድረግ በርካታ ስራዎችን ማከናወን ያስፈልጋል፡፡ እንደ ከዚህ ቀደሙ አይነት ተመሳሳይ ስራዎች ካልተካሄዱ ወረርሽኙ በድጋሚ ማንሰራራቱ አይቀርም፡፡አሁን ባለሙያዎቹ የሚያካሂዱት ግምገማ ይህንን ለማስቀጠልና ክፍተቶችንም ለመድፈን በእጅጉ ይረዳል፡፡
በፌዴራል ኤች አይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ፅህፍት ቤት የእቅድ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት አማካሪው ዶክተር አቻምየለህ አለባቸው እንደጠቆሙት፣ በኢትዮጵያ ለአምስት አመታት ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የኤች አይ ቪ ኤድስ ስትራቴጂክ እቅድ አጠቃላይ የኤች አይቪ ኤድስ ዘርፈ ብዙ ምላሽ ትግበራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ እቅዱ በአለም አቀፍ ደረጃ ከተቀመጡት ግቦች አንፃር በ2030 እ.ኤ.አ ኤች አይቪ ኤድስን ማቆም የሚለውን ራእይ ለማሳካት የተዘጋጀ ነው፡፡ ዋነኛ ማጠንጠኛውም የሶስቱ ዘጠናዎችን ግብ ማሳካትና ተደራሽነትን ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህም በሀገሪቱ ኤች አይቪ ኤድስ በደማቸው ይገኛል ተብለው ከሚገመቱት 653 ሺ ሰዎች ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት ተመርምረው ራሳቸውን እንዲያውቁ፣ ቫይረሱ በደማቸው ከሚገኝ መካከልም 90 በመቶው የፀረ ኤች አይቪ መድሃኒቱን እንዲጀምሩ እንዲሁም 90 በመቶዎቹ በደማቸው ውስጥ ያለው ቫይረስ መጠን በጣም እንዲቀንስ ማድረግን የሚያጠቃልል ነው፡፡
ስትራቴጂክ እቅዱ ማህበረሰቡ ኤች አይቪን በተመለከተ ያለውን ግንዛቤ የማሳደግና ተጋላጭ የሆኑትን የህብረተሰብ ክፍሎችንም በተለየ ሁኔታ ትኩረት በመስጠት የሚከናወኑ ስራዎችን ያጠቃለለ ሲሆን፣ ከሌሎች ሴክተሮች ጋር በጋራ የመስራትን አስተሳሰብ የሚያራምድ ነው፡፡
ዶክተር አቻምየለህ እንደሚገልፁት፤ ግምገማው አለም አቀፍ ልምዶችና ተሞክሮዎች ምን እንደሚመስሉ ለማየት እድል ይፈጥራል፡፡ ይህንንም መሰረት በማድረግ ስትራቴጂክ እቅዱን መከለስ የሚቻል ከሆነ በሽታውን ከመከላከል አንፃር የተሻለ ውጤት ለማምጣት ይረዳል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ስትራቴጂካዊ እቅዱን ለመከለስ የሚያስችለው ግምገማ እየተካሄደ ነው፡፡ ግምገማው በውጭ ሃገር ባለሙያዎች እየተመራ የሚካሄድ ቢሆንም ፣የሃገር ውስጥ ባለሙያዎች ተካተውበት በሰባት ቡድን በመከፋፈል የመስክ ጉብኝት ይደረጋል፡፡ እንድ ቡድን የተለያዩ የሰንድ ምርመራዎችን በማድረግ እቅዱ እንዴት ተግባራዊ ሲደረግ እንደቆየ ይገመግማል፡፡ 67 የሚጠጉ ከሃገር ውስጥ የተውጣጡ ባለሙያዎችም ከውጭ ባለሙያዎች ጋር ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡
እንደ ዶክተር አቻምየለህ ገለፃ ፤ግምገማው ከተጠናቀቀም በኋላ የግምገማውን ውጤት መነሻ በመያዝ ክፍተቶችንና ጥንካሬዎችን በሚገባ በመለየት የኤች አይቪ ስትራቴጂክ እቅዱን የሚከለስ ይሆናል፡፡የእቅዱ ግምገማ ሪፖርት ተጠናቆ ለመውጣት አንድ ወር ይወስዳል፡፡ በአጠቃላይ ከሶስት ወር ባልዘለለ ጊዜ ውስጥ ስትራቴጂክ እቅዱ ተከልሶ ለስራ ዝግጁ ይሆናል፡፡
ግምገማው ሶስቱን ዘጠናዎች ለመድረስ፣ አዲስ በኤች አይቪ ኤድስ የሚያዙትንና የሞት መጠንን ከመቀነስ አንፃር በስትራቴጂክ እቅዱ የተቀመጡ አላማዎችን ለማሳካት የተከናወኑ ተግባሮችን በዝርዝር ነቅሶ ለማውጣት ያስችላል፡፡ በተጠያቂነትና በማስተባበር በኩል የተከናወኑ ስራዎችን ለመለየትም ይረዳል፡፡ ኤች አይቪንና ስርአተ ፆታን አካቶ ከመስራት፣ ሃገራዊ ሃብትን ከማሰባሰብና ስራ ላይ በአግባቡ ከማዋል አንፃር የነበሩ ክፍተቶችንና ጥንካሬዎች ለማወቅም ይረዳል፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

Published in ማህበራዊ

የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት የተቋማትን የማስፈፀም አቅም ለማጎልበት ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል አንዱና ዋንኛው የሥራ አመራር ስልጠና ሲሆን፣ ለአብነትም ከ2004 እስከ 2009 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት ውስጥ በተሰጡ ስልጠናዎች ከ48 ሺ በላይ ሰልጣኞች ስልጠና ማግኘታቸውን የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመለክታል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ሰሞኑን ‹‹በፐብሊክ ሰርቪሱ የስልጠና ሥራ አመራር፣ ፋይዳ፣ ተግዳሮትና የመፍትሔ አቅጣጫ›› በሚል ርዕስ በተካሄደው የጥናት ውጤት ላይ ከተለያዩ ተቋማት ከተውጣጡ አካላት ጋር የፓናል ውይይት አካሂዷል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ መንግሥቱ ይትባረክ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአገሮች መካከል ያለው የእድገት ልዩነት ዋናው ምክንያት አገሮች ለሰው ሀብት ልማታቸው በሚሰጡት ትኩረት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ተወዳዳሪ የሆነ ምርትና አገልግሎት በዓለም ገበያ ሸጦ ኑሮን ለማሻሻልና እድገት ለማምጣት የሚቻለው ይህንን መፍጠር የሚችል የሰው ኃይል ሲኖር ብቻ ነው፡፡
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ መንግሥትም ይህን በመረዳት የተለያዩ የአቅም ግንባታ፣ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲዎች ቀርፆ ተልዕኮውን መሸከም የሚችሉ አቅም ገንቢ ተቋማትንም አቋቁሞ ሰፋፊ ስልጠናዎችንና የአቅም ግንባታ መርሃ ግብሮችን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ ከዚህ አኳያም ባለፉት ሃያ ዓመታት የተሰጡት የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች በአጠቃላይ ተገምግመዋል፡፡ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ግምገማ ወቅት እንደተመለከተው እነዚህ ስልጠናዎችና የአቅም ግንባታ መርሃ ግብሮች የመንግሥትንና የህዝብን አቅም አሻሽለዋል፡፡ ሥርዓቱ የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደመሆኑ ዋንኛ የልማት አጀንዳ ይዞ የሚንቀሳቀሰውና ስትራቴጂክ የልማት ኃይሎችንም እያበቃ ልማቱ እንዲመጣ የሚያደርገው መንግሥት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ የመጣውም እድገት የዚህ የአቅም ግንባታ ውጤት መሆኑ ግለፅ ነው፡፡
ይሁንና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ከመፍጠር አኳያ ግን በድምሩ ሰፊ የሆነ የአቅም ክፍተት እንዳለ አቶ መንግሥቱ ይጠቁማሉ፡፡ ለዚህም ነው የመንግሥት (የፐብሊክ ሰርቪስ) ተቋማት ቀልጣፋና ውጤታማ የሆነ አገልግሎት ለህዝቡ ማድረስ ያልቻሉት እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግር ዝንፈት እየታየ ያለው ሲሉ ያብራራሉ፡፡
እንደ አቶ መንግሥቱ ገለፃ፤ የዎርክሾፑ ዋና ዓላማ ከዚህ ቀደም የተሰጡ ስልጠናዎች፣ አመራራቸውና ፋይዳቸው ላይ ምን ችግሮችና ስኬቶች አሉ የሚለውን ለማየትና የተገኙ ስኬቶችን በመያዝ ችግሮችን በመፍታት ውጤታማ የሆነ የስልጠና አመራር ሥርዓት መፍጠር ነው፡፡ ስለዚህም አጀንዳው የጋራ ነው፡፡ ስልጠናው ፋይዳ እንዲኖረው ሁሉም አካላት ተጋገግዘው መሥራት ይጠበ ቅባቸዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የውይይቱ ዓላማ ከሆኑት መካከል አንዱ የሠራተኞችን ብቃት ለመጨመር የሚሰጡ የሥራ አመራር ስልጠናዎች ሰልጣኞች በሥራቸው ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያመጡ ለማድረግ ሲሆን፣ ስልጠናዎቹ ያስገኙትን ፋይዳ ማመላከትም ጭምር ነው፡፡
የሥልጠና ሥራ አመራሩ ፐብሊክ ሰርቪስ ሴክተሩ ያሉበትን ክፍተቶች ለመለየትና ለተለዩት ችግሮች ምክረ ሀሳብ ማመለከትም የውይይቱ ሌላ አላማ እንደሆነ ከጥናቱ አቅራቢ አንዷ የሆኑት ከፍተኛ አማካሪዋ ሃይገት አድሃና ተናግረዋል፡፡ ጥናቶቹም ትኩረት ያደረጉት የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት በሰጣቸው ስልጠናዎች ላይ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ጥናት አቅራቢዋ ገለፃ፤ ስልጠናዎች ያስገኙት የግብ ስኬት መገለጫዎች ከሆኑት መካከል አገልጋዮች ሰዓት በማክበር ተገልጋይን በተሻለ በማገልገል መነሳሳት ማሳየታቸው በዚህም የተገልጋይ እርካታ እንዲጨምር ማድረግ መቻል የሚሉት ይገኝበታል ፡፡
ከታህሣስ ወር 2006 ዓ.ም እስከ ሐምሌ ወር 2008 ዓ.ም የተሰጡ ተቋም ተኮር ስልጠናዎች ከሰልጣኞች አኳያ ያስገኙት ፋይዳ ሲታይ የሥራ ተነሳሽነት፣ ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ጥረት ለማድረግ የሚረዳ የዕይታና የሥራ ባህል ለውጥ ማምጣት ተችሏል፡፡ በአገልግሎት ሰጪዎች ባህሪ ላይ በመጣው ለውጥ ምክንያት የተገልጋይ ቅሬታ መቀነስ የቻለ ሲሆን፣ በለውጥ መሣሪያዎች ዙሪያ ተመሳሳይ አረዳድ መፍጠር መቻሉንም ጥናት አቅራቢዋ ተናግረዋል፡፡ የመሪዎች የመምራት ዕይታም ለውጥ ማምጣቱን አመልክተዋል፡፡
በስልጠና ሥራ አመራር ዙሪያ በፐብሊክ ሰርቪስ ተቋማት የሚታዩ ችግሮች እንዳሉም ከፍተኛ አማካሪ ሃይገት በጥናታቸው አመልክተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የስልጠና ፍላጎት ዳሰሳ ጥናት የግንዛቤ ውስንነትና ትኩረት ማነስ መታየቱን ጠቅሰዋል፡፡ የስልጠና ርዕሶችን በጥናት ላይ ተመስርቶ አለመምረጥ፣ ስልጠናዎችን አቅዶ አለመንቀሳቀስና ሰልጣኞችን በአግባቡ አለመልመል ሌላው ችግር መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ሰልጣኞችን በሂደቱ ከመጀመሪያ አንስቶ አለማሳተፍና በስልጠናው ዲዛይን ላይ ያለ ተሳትፎ ውስን መሆንም በችግርነት የሚካተቱ ናቸው፡፡ በተጨማሪም የስልጠናው ሂደት ክትትልና ድጋፍ ደካማ ሲሆን፣ ሰልጣኞች ከስልጠና ያገኟቸውን ትምህርታዊ ነጥቦች የመገምገሚያ ሥርዓት የለም፡፡ በስልጠና የተገኘ ዕውቀትን ወደ ሥራ ቦታ ለማሸጋገር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር አኳያም ውስንነት ያለ ሲሆን፣ የስልጠናዎችን የግብ ስኬትና ፋይዳ አለመገምገም በችግርነት ተጠቅሷል፡፡ እንዲሁም ከፍተኛ አመራሮች ምሳሌ አለመሆን በተለይ ደግሞ የስልጠና ፖሊሲዎች አለመኖርም በችግር ውስጥ የሚካተቱ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ጥናት አቅራቢዋ እንደሚሉት ፤ በስልጠና ሥራ አመራር ዙሪያ በስልጠና ሰጪ ተቋም ዘንድ የታዩ ችግሮችም አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የስልጠና ርዕሶች የፐብሊክ ሰርቪሱን ተጨባጭ ችግሮች የሚለይ ጥልቀት ያለው ጥናት ላይ የተመሰረቱ አለመሆን ተጠቃሹ ነው፡፡ የስልጠና ፍላጎት ዳሰሳ ጥናት በጥልቀት በቂ ጊዜ ሰጥቶ ወጥነት ባለው መልኩ አለማከናወንና ሰልጣኞች ለስልጠናው ተገቢ መሆናቸውን ማረጋገጫ ሥርዓቱ የላላ መሆንም በችግርነት የሚገለፁ ናቸው፡፡ እንዲሁም ተገልጋይ ተቋማት በስልጠና ዝግጅቱ ሂደት በስፋት አለማሳተፍና ተገቢውን አሰልጣኝ አለመመደብ፣ የድህረ ስልጠና ክትትል ሥርዓት አለመኖር፣ በስልጠና የተገኙ ትምህርታዊ ነጥቦች ወደ ሥራ ቦታ ለማሸጋገር የሚያስችል ድጋፍ አለማድረግና የስልጠናዎችን ግብ፣ ስኬትና ፋይዳ ግምገማ ሥራዎች ውስንነት ያለበት መሆኑ በችግርነት ተመልክተዋል፡፡
ከፍተኛ አማካሪዋ፣ መፍትሄ ብለው ካቀረቧቸው መካከልም ተገልጋይ ተቋማቱ በስልጠና ሥራ አመራር በቂ ዕውቀትና ክህሎት ያለው አስተባባሪ (ባለሙያ) ኃላፊ የመመደብ አስፈላጊነት አንዱ ነው፡፡ የስልጠና መመሪያ ማዘጋጀትና ስልጠናን በዕቅድ መምራትም ሌላው መፍትሄ ነው ብለው ያስቀመጡት ሐሳብ ነው፡፡ በቂ የቅድመ ስልጠና ዝግጅት ማድረግ እንዲሁም ለሥራ መደቦች የብቃት ማዕቀፍ ማዘጋጀትም በመፍትሄነት የጠቆሙት ሲሆን፣ በተጨማሪም ሰልጣኞች የወሰዱትን ስልጠና በሥራ ገበታቸው ያገኙትን ትምህርት ሪፖርት እንዲያደርጉና ለመተግበር የሚያስችል ዕቅድ እንዲያዘጋጁ ማድረግም መፍትሄ ነው ካሏቸው ውስጥ የሚካተት ነው፡፡
ጥናት አቅራቢዋ ለስልጠና ሰጪ ተቋማት መፍትሄ ያሏቸውንም ሲጠቁሙ እንደገለፁት፤ የአፈፃፀም ምዘናዎችን ለስልጠናዎች መነሻ ማድረግ፣ የፐብሊክ ሴክተሩን ተጨባጭ ችግሮች መሰረት ያደረጉ የስልጠና ርዕሶችን መለየት፣ በሰልጣኞች ስልጠናው ተገቢ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ሥርዓት መዘርጋት፣ የሰልጣኞች ቁጥር ለስልጠናው ውጤታማነት በተቀመጠው ስታንዳርድ መሰረት ብቻ እንዲሆን ማድረግ እንዲሁም ሰልጣኞች የወሰዱትን ስልጠና በሥራ ገበታቸው ለመተግበር የሚያስችል ዕቅድ እንዲያዘጋጁ ማድረግና የድህረ ስልጠና ግምገማ ሥርዓት ማበጀት ያስፈልጋል፡፡
ሌላው የጥናቱ አቅራቢ ተባባሪ አማካሪ የሆኑት አቶ አለማየሁ አሰፋ በበኩላቸው፤ ‹‹ሰውን ሰው ያደረገው እቁብ ነው›› የሚለውን የተለመደውን አገርኛ አባባል ተውት አድርገው ‹‹ሰውን ሰው የሚያደርገው ስልጠና ነው›› በሚለው በመተካት የስልጠናን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተው አስረድተዋል፡፡ በጥናቱ እንዳረጋገጡትም ሰልጣኞች ከስልጠናው በኋላ እውቀት በማግኘታቸው የሚሠሩባቸው ተቋማት ደንበኛ ቅሬታው ቀንሷል፡፡
‹‹በእርግጥ ስልጠና ለሁሉም ችግር መፍትሄ አይሆንም›› የሚሉት አቶ አለማየሁ፣ መፍትሄ እንዲኖር ካስፈለገ የሥርዓት መስተካከል ሊኖር እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡ አንዳንድ የተቋም ሠራተኞች ቢ.ፒ.አር እና ቢ.ኤስ.ሲ የኢህአዴግ ፍልስፍና ይመስላቸዋል፡፡ ከዚህም የተነሳ ለመተግበር ቸል ሲሉ ይታያሉ፤ ነገር ግን ሁለቱም ጽንሰ ሐሳቦች ምሁራን የቀመሯቸው የአስተዳደር መቀመሪያ መሣሪዎች በመሆናቸው በአግባቡ ቢተገበሩ ውጤታማ የሚያደርጉ ስለመሆናቸው ያብራራሉ፡፡
ጥናት አቅራቢው አቶ አለማየሁ እንደሚ ናገሩት፤ መንግሥት የስልጠናን አስፈላጊነት አምኖ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ፕሬዚዳንቶችንና ምክትል ፕሬዚዳንቶችን ጨምሮ በተዋረድ ላሉ ምሁራንም አስፈላጊው ስልጠና እንዲሰጥ በማደረግ ላይ ነው፡፡ ይሁንና ለእነዚህ ምሁራን የሚመጥን አሰልጣኝም ከግምት ውስጥ በማስገባት አውሮፓን ጨምሮ ከሌሎች አገራት እንዲመጡ ቢደረግም ስልጠናው የሚመለከታቸው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አሊያም ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኖ ሳለ የሚልኳቸው ግን የሌላ ዘርፍ ኦፊሰሮችን አሊያም ጉዳዩ የማይመለከታቸውን አካላት ነው፡፡ በአንፃሩ ግን አንድ የውጭ አገር ጉዞ አለ ሲባል በቦታው ቀድመው የሚገኙት ራሳቸው ናቸው፡፡ እንዲህ አይነቱ አካሄድ የተያዘውን ግብ ለማሳካት እንቅፋት እንደሚሆን ከግንዛቤ ውስጥ መግባት ይኖርበታል፡፡
የፓናል ውይይቱ ተሳታፊ ተወያዮች በተለያየ መንገድ ስልጠናዎችን የሚሰጡ አካላትም እንደ መሆናቸው ገጠመኞቻቸውንም በማከል ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አንስተዋል፡፡ አጥኚዎቹ ምን ያህል ተቋማትን ወስደው ጥናቱን እንዳካሄዱ፣ ስልጠናን አስመልክቶ ፖሊሲ ለማዘጋጀት የሚያስችል ሰነድ ተጀምሮ እንደነበርም በመጥቀስ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል፡፡
እስካሁን የተለያዩ ስልጠናዎች እየተሰጡ ቢሆንም፤ ደንበኞቹን በማርካት በኩል ሊነገርለት የቻለ አንድ የሰነዶችና ውል ማረጋገጫ ተቋም ብቻ ለምን ሆነ ? ሌሎቹ እንደ መብራት ኃይልና መሰል ተቋማትስ ስለምን የተሻለ በመሥራት መልካምነ ታቸውን አላረጋገጡም? የሚሉ ጥያቄ አዘል አስተያየምትም ሰንዝረዋል፡፡
በተለይም ጥናቱ ችግሮች ናቸው ብሎ ካስቀመ ጣቸው መካከል በየተቋሙ ስላለው የግልፅነት አለመኖር በችግርነት አለማነ ሳቱን በአስተያየታቸው ተናግረዋል፡፡ በአንድ ተቋም ውስጥ ያለ አንድ ሠራተኛ ለተቋሙ ለውጥ በማሰብ ሐሳብና አሰተያየት ሲሰነዝር ‹‹የአመለ ካከት ችግር አለብህ›› የሚል ፍረጃ ውስጥ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ ከዚህም የተነሳ በአብዛኛው በተቋሙ ውስጥ የሚኖረው እንቅስቃሴ የበላይ አመራሩን ለማስደሰት የሚደረግ ሩጫ ስለመሆኑም ነው ያስረዱት፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ከአንድ ተቋም እንዲሰለጥን የሚላከው ተገቢው ሰው ሳይሆን ‹‹እስኪ እገሌ ዘና ብሎ ይምጣ›› በሚል አመለካከት የሚሄድ በመሆኑ ተፈላጊውን ውጤት ማምጣት እንደ ማይቻልም ተሳታፊዎቹ ያመለክታሉ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ለዋና ኃላፊዎች ተብሎ በሚዘጋጅ ስልጠና ላይ ካሜራ የማይኖር ከሆነ ኃላፊዎቹ ስልጠናውን እንደማይካፈሉትም ተጠቁሟል፡፡ በስልጠና ስም የሚወጣው ገንዘብም ብክነት የሚታይበት መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡
ተወያዮቹ በአንዳንድ ቦታ በሚያሰለጥኑበት ወቅት የታዘቡትን አስመልከተው እንደተናገሩት ከሆነ፤ የአንዳንድ ተቋማት መሪዎችን ጨምሮ የተቋማችሁን ርዕይ አሊያም ተልዕኮ ፃፉ በሚባሉበት ወቅት ጭርሱኑ የማያውቁት ሆነው ተገኝተ ዋል፡፡ በዚህ አይነትማ የአገሪቱን ዋና ዓላማ በጭራሽ የሚያውቁት አይመስላቸውምና አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ አግኝተ ውታል፡፡
ከውሃ፣ መስኖና ኤሌክ ትሪክ ሚኒስቴር የተገኙት አቶ ሰለሞን ወርቅነህ፣ የራሱን ተቋም ርዕይ የማያውቅ አንድ ሰልጣኝ የአገርን ርዕይ በፍፁም ሊያውቅ አይችልም ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የመጡት አቶ ትካበ ረዳ በበኩላቸው፤ ምንም እንኳ ተግዳሮቶች ቢነሩም፣ የስልጠና ፋይዳ ጉልህ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ አንድ ጫማ ከፋብሪካ ሲወጣ ምቹና አስደሳች ሊሆን እንደሚችል ሁሉ አንድ ምሩቅም ከዩኒቨርሲቲ ሲወጣ የተሻለ አቅም እንደሚኖረው ይናገራሉ፡፡ ጫማውም በተሻለ እንዲያገለግልና እንዲዋብ በየተወሰነ ጊዜ የጫማ ቀለም እንደሚያስፈልገው ሁሉ ምሩቁም በሥራ ዓለም እያለ የተሻለ ማገልገል እንዲችል ተከታታይነት ያለው ስልጠና እንደሚያስፈልገው ነው የተናገሩት፡፡
አቶ ትካበ፣ በአንዳንድ ተቋም ከአለቃው ይልቅ ፈፃሚው በተሻለ እንደሚያገለግል ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ምንም እንኳ ከእኔ ጡንቻ የእርሱ ቢበልጥም የእኔ አለቃ ስለተኛ እኔ መተኛት የለብኝም›› ሲሉ ነው አስተያየታቸውን የገለፁት፡፡
ተባባሪ አማካሪው አቶ አለማየሁ በማጠቃለያቸው ወቅት እንደተናገገሩት፤ እንደ ውይይቱ ተካፋዮች ሁሉ እርሳቸውም ሲያሰለጥኑ ብዙ ነገሮችን ታዝበዋል፤ ስልጠና ሲባል ‹‹ስንት ነው የሚከፈለኝ›› የሚል የአመለካከት ቸግር መኖሩን ነው ጠቅሰው፣ ‹‹እሱን ለማሰልጠን ካልከፈልከው አይመጣም›› ሲሉም ነው የሚገልፁት፡፡
አንዳንዶች ደግሞ ኢንስቲትዩቱ እነሱን ለማሰለጠን ብቃት እንደሌለው አድርገው የሚያስቡ መሆናቸውንም ይናገራሉ፡፡ እዚህ ላይ ልክ ናቸው የሚያስብል አተያይ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ለዚህም በምክንያትነት ያስቀመጡት እንደ ኢትዮ ቴሌኮም አና መብራት ኃይል የመሳሰሉ ውስብስብ ተቋማትን ለማሰልጠን ራሱን የቻለ ቴክኒካዊ ሙያን ጠንቅቆ ማወቅ መጠየቁን ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም አሁን በደረሰበት ቴክኖሎጂ ‹‹አካሄድህ እንዲህ መሆን አለበት›› ተብሎ ማሰልጠን ይቻላል ወይ ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡
የኢትየዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ደግሞ በሁሉም መስክ ብቃት ያላቸው አሰለልጣኞች አሉት ብሎ በድፍረት መናገር እንደሚከብድም ነው የሚያመለክቱት፡፡ አንዳንዴም ወደነዚህ አይነት ተቋማት ሲኬድ ተቋማቱ፣ ‹‹ከኢንስቲትዩቱ አሰልጣኞች መጥተው የነበረ ቢሆንም ከእነሱ ይልቅ ግን የአኛ ቴክኒሺያኖች ይሻላሉ›› ሲሉ እንደሚደመጡም አቶ አለማየሁ አልሸሸጉም፡፡ በመሆኑም በእንደነዚህ አይነት ተቋማት ላይ የአስተዳደር ጥቅል ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር የጥራትን ጉዳይ ጠለቅ ብሎ ለማሰልጠን አስቸጋሪ በመሆኑ ሊታሰብበት የተገባ ጉዳይ እንደሆነ ነው የጠቀሱት፡፡
አቶ አለማየሁ፣ ‹‹ምን ያህል ሰዎችን ለጥናታችሁ መሰረት አደረጋችሁ›› ተብሎ ለተነሳው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ እንደተናገሩት፤ በጥቅሉ በተወሰደው የጊዜ ገደብ ውስጥ ከሰለጠኑት ወደ 15 ሺ ያህል ሰልጣኞች መካከል የተወሰዱት ሦስት መቶ ሰልጣኞች ናቸው፤ እነዚህም የተመረጡትበት መስፈርት ተከታታይ ስልጠና የወሰዱ በመሆናቸው ነው፡፡
‹‹ስልጠና ግራም ነፈሰ ቀኝ ውጤት ያለው ስለመሆኑ አይካድም›› የሚሉት አቶ አለማየሁ፣ ከምንም በላይ ደግሞ ተከታታይ ስልጠና ውጤታማ የሚያደርግ መሆኑን በእርግጠኝነት ገልፀዋል፡፡ ለአብነትም የኢትዮጵያን አየር መንገድ ስኬታማ ሊያደርግ የቻለው ተከታታይ ስልጠና ስለመሆኑ ነው ያስረዱት፡፡ ስለዚህም ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ በስልጠና እንዴት ይበልጥ ውጤታማ መሆን ይቻላል የሚለው መሆን እንዳለበት ያመለክታሉ፡፡
ከፍተኛ አማካሪዋ ሃይገት በበኩላቸው፤ ትኩረት ሊደረግ የሚገባው ስልጠና በእርግጥ ለውጥ ያመጣል የሚለው ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ስልጠና እንደ አንድ የሰው ሀብት ልማት ማብቂያ ተደርጎ መታሰቡ ላይ መሰረታዊ የሆነ ችግር እንዳለ አመልክተዋል፡፡ የሰው ሀብት ልማት ላይ የሚቀመጡ ለሙያዎች ብቁ ቢሆኑ እንደሚመረጥም ነው አስተያየታቸውን የገለፁት፡፡
አስተያየታቸውን የሰጡ ተወያዮች እንደተናገገሩት ሁሉ ጥናት አቅራቢዋም በስልጠና ላይ ተገቢውን ሰው ያለመላክ ችግር በሰፊው መስተዋሉን በጥናታቸው ወቅት ያጋጠማቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በሌላ በኩል ምቹ የሆነ አካባቢያዊ ገፅታን በመፍጠሩ በኩል ችግር መኖሩን ጠቅሰው፤ በተለይም ሐሳብን በነፃነት በመግለፁ በኩል ያልተፈቱ ነገሮች መኖራቸው ከተወያዮቹ መነሳቱ ዕውነት መሆኑን ነው የተናሩት፡፡ ሰልጣኞች በስልጠናው ወቅት ያገኙትን ለመተግበር ሲሞክሩ ያለመደመጥ ችግር የሚያጋጥማቸውና የአመለካከት ችግር አለባችሁ የሚባሉ ከሆነ ለአሰልጣኙም ሆነ ለሰልጣኙ ድካም በመሆኑ የሰው ሀብት ልማቱ መላ ሊል የተገባው እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ በተጓዳኝ ከስልጠና በኋላ ተቋማት ለተገልጋዮች ምን መልካም ነገር አመጡ የሚለውም መታየት ያለበት እንደሆነ አክለው ገልፀዋል፡፡
በተወያዮቹ የተነሱ አስተያየቶች መልካምና ለኢንስቲትዩቱም እንደ ግብዓት የሚያገለግሉ መሆናቸውን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ መንግሥቱ ይገልፃሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ በአንድ ተቋም ውስጥ ነፃ የሆነ የሐሳብ መንሸራሸር ከሌለ አንድ ነፃ የሆነ አቋም ይዞ ለመውጣት ያዳግታል፡፡
‹‹በአገሪቱ በርካታ የአቅም ግንባታ መርሃ ግብሮች ተካሂደዋል፤ በግንዛቤ ደረጃ የተለያየ አቅም መፍጠር ተችሏል፡፡ አገሪቱም ከዚህ ደረጃ ላይ ለመድረሷም ግልፅ የሆነ የአቅም ግንባታና ስትራቴጂ ፖሊሲ በመነደፉ ነው፡፡ እነዚህን ተግባራዊ የሚያደርጉ ተቋማት ከዩኒቨርሲቲ ጀምሮ በስፋት ተቋቁመው፣ የስልጠና ተቋማትም ተቋቁመው ነው እዚህ ደረጃ ላይ የደረስነው›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ ለለውጡ እውቅና መስጠቱ መልካም መሆኑን ጠቅሰው፣ በርካታ ችግሮች መኖራቸውንም ነው የሚናገሩት፡፡
አቶ መንግሥቱ፣ ‹‹ለምንድን ነው የሰነዶችና ውል ማረጋገጫ ተቋም ብቻ ውጤታማ መሆን የቻለው?›› ሲሉ ይጠይቁና፣ ውጤታማ እንዲሆን ለተቋሙ የተለየ ምቹ ሁኔታ እንዳልተፈጠረ ነው የተናገሩት፡፡ ‹‹ውጤታማ መሆን የተቻለው የተቋሙ አመራርና ሠራተኛ የሚባለውን ወስደው በራሳቸው አካሄድ መስዋዕትነት ከፍለው በመሥራታቸው ነው›› ብለዋል፡፡ ሁሉም ደግሞ የየራሱን መንገድ በመፈተሸ ለውጤታመነቱ ሊተጋ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡ ‹‹አንዳንዶቻችን ወደ ሌላኛችን ችግሮችን ልንወራወር አይገባም፤ ምክንያቱም ሁላችንም የዚህ ሥርዓት አካል እንደመሆናችን ይመለከተናልና ቸል ልንል አይገባም›› በማለትም አስገንዝበዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ አመራሩ ግን ለሁሉም ነገር ወሳኝ ነው፤ አዲስ ቅኝትና አካሄድ በመፍጠር ውጤታማ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ ለአንድ ተቋም በመልካምም ሆነ መጥፎ መቀየር አመራሩ ድርሻው የጎላ ነው፡፡፡ ለሰው ሀብት ልማት የሚሰጠው አመለካከት በተቀየረ ቁጥር ሁኔታዎች ይቀያየራሉ፡፡ ለአንድ ተቋምም ሆነ አገር መለወጥ ግልፅነት ጠቃሚ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የለውጥ መተግበሪያ መሣሪያዎችም ወሳኝ ናቸው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ያዝ ለቀቅ ሊደረጉ አይገባም፡፡

አስቴር ኤልያስ

Published in ፖለቲካ

በሀገራችን የትራፊክ አደጋ የሚያደርሰው ጉዳት በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል፡፡ በርካታ ዜጎች በአደጋው ሳቢያ እንደወጡ ቀርተዋል፡፡ ሀብትና ንብረታቸውም ወድሟል፡፡ ሀገሪቱም በአደጋው ሳቢያ ስሟ በመጥፎ እየተጠቀሰ ሲሆን ፣ እያጣች ያለችው የሰው ሀይልም ሆነ ሀብት በቀላሉ የሚገልጽ አይደለም ፡፡
ለአደጋው በርካታ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር፣ የአመራሩ በሃላፊነት ስሜት አለመምራት፣ ተቀናጅቶ አለመስራት፣ ተጠያቂነት አለመኖር፣ እንዲሁም በአሽከርካሪው ዘንድ የሚታየው ግዴየለሽነት እና የስነ ምግባር ጉድለት ሌሎች ምክንያቶች ናቸው፡፡ ለአዳዲስ መንገዶች ተገቢው ምልክት አለመደረጉ፣ ምልክቶች ከቦታቸው ሲነሱም ምትክ አለማድረግም ሌሎች ምክንያቶች ናቸው፡፡
እኛም የትራፊክ አደጋ የሚከሰትባቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው፤ ችግሮቹን ለመፍታት እንዴት አልተቻለም የሚሉ የተለያዩ ጥያቄዎችን በትራንስፖርት ባለስልጣን የመንገድ ደህንነት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ለሆኑት አቶ ደረጀ ወልደዮሀንስ አንስተን የሰጡንን ምላሽ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።

አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ እየተከሰተ ለሚገኘው የትራፊክ አደጋ ዋና መንስኤ ምንድን ነው?
አቶ ደረጀ፡- በዋናነት የመንገድ ትራፊክ አደጋ እንዲከሰት ምክንያት እየሆነ ያለው ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር ነው። ፍጥነት ከምን ይመነጫል፤ አሽከርካሪዎች ለምን ይፈጥናሉ የሚለውን ማየት መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ አሽከርካሪዎች የሚሰለጥኑበት ጊዜ በቂ ባይሆንም እንዴት ማሽከርከር እንዳለባቸው ይነገራቸዋል። ሆኖም በርካታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ፍጥነት ችግር እየሆነ የመጣው የአሽከርካሪዎች ባህርይ ጉዳይም ስላለበት ነው።
ፍጥነት ከእኛ አገር የመንገድ ትራፊክ ባህርይ አንጻር ሲታይ የመንገዶቹ ጥራት ጉድለት በእነዚህ ላይ ፍጥነት ሲደመር በጣም አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ ከባድ አደጋዎችንም እያስከተለ ይገኛል።
ፍጥነት የማሽከርከር ብቃት ማሳያ አይደለም ፤ በተለይም ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች አንጻር በጣም ከባድና ሰውንም አገርንም ለችግር የሚዳርግ ነው። በአነስተኛ ሁኔታ በተቀመጠው የፍጥነት ወሰን መሰረት መሄድ በተቻለ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ አደጋን መከላከል ይቻላል፡፡ አደጋ ቢፈጠር እንኳን በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ሊደርስ የሚችለውን ውድመት ለመቀነስ ሰፊ እድል ይኖራል።
አዲስ ዘመን፡- ፍጥነት ባህርይ እንዳይሆን በምን መልኩ ነው መከላከል ወይም መቆጣጠር የሚቻለው?
አቶ ደረጀ፡- ይህ የፍጥነት ባህርይ ወይም ችግር ሊቀረፍ የሚችለው በስልጠና ነው፤ ለአሽከርካሪዎች አሁን እንደምናየው የለብለብ ሳይሆን በቂ ጊዜ ተወስዶ ተገቢው የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠና መሰጠት ይኖርበታል። በስልጠናው የቀሰሙትን እውቀት ወደ መንገድ ሲወጡ በትክክል ተግብረውታል ወይ? የመንገድ ላይ ህጎችና ደንቦችን አክባሪ ናቸው ወይ? የሚሉትን ለማወቅ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግም ያስፈልጋል። ይህንን በማድረግ በፍጥነት ምክንያት የሚከሰቱትን አደጋዎች ማስቀረት እንኳን ባይቻል በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ግን ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ፍጥነት የብዙ አደጋዎች መነሻ ነው ካልን በአገር አቀፍ ደረጃ የአደጋው ሁኔታና ያሳደረው ጫና እንዴት ይገለጻል?
አቶ ደረጀ፡- ለመንገድ ትራፊክ አደጋ ፍጥነት ዋናው መንስኤ ቢሆንም ሌሎች በርካታ ምክንያቶችም አሉ፡፡ ፍጥነት የሚያስከትለው ውድመት ግን ወደር አይገኝለትም፡፡ በአገሪቱ እየደረሰ ያለው የትራፊክ አደጋ ያስከተለው ውድመት በውል አይታወቅም፤ ታውቋል ተብሎ ሪፖርት የሚደረገውም ቢሆን ከእውነታው በእጅጉ ያንሳል፡፡ ለዚህም በርካታ ምክንያቶች አሉ። አደጋዎችን በወቅቱ ከስር ከስር ተከታትሎ ሪፖርት ማድረግ የሚያስችል እውቀት ፣ አደረጃጀትና አሰራር በጣም ዝቅተኛ ነው። ይህ በአንዳንዱ ዘንድ የለም የሚባልበት ደረጃ ላይ ይገኛል።
ይህ ችግር በመንገድ ትራፊክ አደጋ የሚደርስብንን ኪሳራ እንዳናውቀው አድርጎናል። ይህንን ስራ ይሰራሉ ተብለው የተቀመጡ እንደ ፖሊስ፣ ትራፊክ ፖሊስና ሌሎች ህግ አስከባሪዎች ያሉ አካላት የማይደርሱባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች አሉ፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የሚሞተው ሰውና የሚጠፋው ንብረት አይመዘገብም። አካላቱ በሚደርስባቸው ቦታዎች ላይም ቢሆን የህግ አስከባሪዎቹ በመንገድ ላይ በማይኖሩበት እንደ ሌሊት ባሉት ጊዜያት የሚደርሱ አደጋዎችም አይመዘገቡም፡፡
የሚገርመው በመንገድ ላይ መኪኖች ሲጋጩ ጉዳቱ በሰው ላይ እስካልደረሰ በሚል ብቻ እንስማማ በማለት ሪፖርት ሳይደረግ ይቀራል። እዚህ ላይ የትራፊክ ፖሊሶችም ጭምር ሲተባበሩ ይስተዋላል።
በዚህ ምክንያትም በቀን፣ በወር እንዲሁም በዓመት በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ምን ያህል አደጋዎች ደረሱ? በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይስ ምን ያህል ጉዳት ደረሰበት የሚሉት አይታወቁም።
ተሽከርካሪዎችና መለዋወጫቸውን ጨምሮ ወደ አገሪቱ የሚገቡት በውጭ ምንዛሪ ተገዝተው ነው፤ የውጭ ምንዛሪ ለእኛ ውድ እንደሆነ ሁሉም በሚገባ ይገነዘባል። በመሆኑም በመንገድ ትራፊክ አደጋ የሚደርሱ ጉዳቶች በትክክል ሊመዘገቡ ይገባል።
ከዚህ ባልተናነሰ መልኩ ችግር ሆኖ ያለው አደጋዎቹም፣ የሞተው ሰው የጠፋው ንብረት ሁሉም ታይቶ የሚሰጠው ግምትና የሚወጣው ሪፖርት የማይመጣጠን እና እጅግ የወረደ መሆኑ ነው። ይህ የሚፈጠረው አንድም ከእውቀት ማነስ አሊያም ከሌብነት ጋር በተያያዘ ነው።
በመንገድ ትራፊክ አደጋ የሚሞቱ ሰዎች ለአገር ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከእውቀታቸው በማህበረሰቡ ውስጥ ካላቸው ተቀባይነት አንጻር እየታየ ሪፖርት አይደረግም «አንድ ሰው ሞተ ተብሎ ብቻ ተብሎ ሪፖርት መቅረቡ ላይገልጻቸው የሚያጎሉትን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አስተዋጽኦም ላይለካው ይችላል።
በሌሎች ሀገሮች በዚህ አይነት መልኩ አይደለም ሪፖርት የሚደረገው፡፡ ሰውየው ያበረከተው ወይም ቢኖር የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ይተመናል፤ አገር አሱን በማጣቷ የሚደርርስባት ኪሳራም ይሰላል። ይህም በእኛ አገር ባለመኖሩ ያልተሟላ የሪፖርት አያያዛችን መገለጫ ነው።
በጥቅሉ በአገሪቱ እየደረሰ ያለው የመንገድ ትራፊክ አደጋ በሞትም በከባድ ጉዳትም በንብረት ላይ እየደረሰ ባለው ጉዳት እጅግ በወረደ መልኩ ነው ሪፖርት እየተረደገ ያለው። ይህ ችግሩን በአግባቡ ተረድቶ መፍትሔ የማፈላለጉን ስራ ምሉዕ እንዳይሆን አድርጎታል።
አዲስ ዘመን፡- ከአደጋው ስፋትና እያደረሰ ካለው ቀውስ አንጻር ሪፖርት አያያዙን ለማዘመን ባለስልጣኑ ምን እያከናወነ ነው?
አቶ ደረጀ፡- የተለያዩ ጥረቶች ይደረጋሉ፤ ግን በቂ ናቸው ማለት አይቻልም። ዘርፉን እናስተካክለው ካልን በዘርፉ የሰለጠነና እውቀት ያለው የሰው ኃይል ማብዛት ያስፈልጋል። እውቀቱ በትራንስፖርት ዘርፉ እንዲሁም ህግ አስከባሪ በሆኑት አካላትም ዘንድ ሊኖር ይገባል፤ እነዚህን አካላት አብቅተን በቂ ስልጠና እና ግብዓቶች ማሟላት መቻል ይኖርብናል፤ አሰራሩን የሚያግዝ አደረጃጀት ማመቻቸትም ያስፈልጋል፤ ደረጃውን የጠበቀና በትክክል ችግሩን ያገናዘበ ግምትም መሰራት ይኖርበታል፤ ይህ ሁሉ አደጋው በአገር ላይ ያደረሰውን ውድመት በማወቅ የመፍትሔው እርምጃም በዚሁ መሰረት እንዲሆን ማድረግ ያስችላል፡፡ ችግሮችን የመቋቋም ሃይልም ይፈጥራል።
ይህንን ለማድረግ በአሁኑ ወቅት መንግስት የጀማመራቸው ስራዎች አሉ። ስራዎቹ በቁርጠኝነት የሚኬድባቸው በመሆኑ ውጤቱን መለካት የሚቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትራንስፖርት ሳይንስ ዘርፍ ስልጠናዎችን መስጠት የጀመሩበት ሁኔታ አለ፡፡ የትራፊክ ህግ ማስከበሩን በሚሰሩ አካላት ዘንድም ካለው ችግር ጋር ይመጣጠናል ባያስብልም ስልጠናዎች ከቀድሞው በተሻለ መልኩ እየተሰጡ ነው። ሌሎች አገሮች የትራፊክ ፖሊሶቻቸውን እስከ ሶስተኛ ዲግሪ (ፒኤችዲ) ድረስ የሚያስተምሩበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ እነዚህ ጉድለቶችና የተሰጠው ትኩረት እጅግ ዝቅተኛ መሆን ችግሮችን እያባባሰ ነው። በመሆኑም መንግስት የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ ካልቀጠለ በትራፊክ አደጋ ምክንያት ብቻ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከባድ ችግር ውስጥ ይወድቃል።
በዘርፉ ኪራይ ሰብሳቢነት (ሌብነት) ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱም ሌላው ችግር ነው። አሽከርካሪው ቤቱ ሆኖ መንጃ ፍቃድ ይገዛል ፤ የስልጠና ተቋማት የሚባሉትም በሚፈልጉት መልኩ የማሰልጠኛ ሥርዓተ ትምህርቱን እየሸራረፉ ይጠቀማሉ፤ ወደ አገሪቱ የሚገቡ ተሽከርካሪዎችም ያረጁ ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የተሽከርካሪ ብቃት በአመት አንዴ ይመረመራል ይባላል እንጂ በአግባቡ አይከናወንም፡፡ አሰራሩ በሙስና የተተበተበ ነው፤ ይባስ ብሎም አንዳንድ ክልሎች ላይ ምንም ዓይነት የብቃት ምርመራ የማይደረግበት ሁኔታ ይስተዋላል። ከሌሎች አገሮች ያረጁና የተጣሉ ተሽከርካሪዎችን እየገዛን ወደ ሀገራችን ማስገባታችን ሳያንስ በአግባቡ ሳንመረምራቸው ወደ መንገድ እንዲወጡ እናደርጋለን፤ መልሰው እኛኑ ይገሉናል ፤ የአገር ሀብትን ያወድማሉ።
አዲስ ዘመን፡- የትራፊክ አደጋ በአገሪቱ አሳሳቢ ከሆኑ ችግሮች መካከል ትልቁን ስፍራ ይዟል፤ ይህን ለመከላከል ህብረተሰቡን በማስተማር ላይ ምን ለመስራት ታቅዷል?
አቶ ደረጀ፡- ሀገራችን በዚህ በኩል ትንሽ የተራመደች ትመስላለች። ጥሩ እየተሰራ ነው። በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት፣ የኃይማኖት አባቶች ፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች እንዲካተቱ በማድረግ የማስተማሩ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል።ይህም በተወሰነ መልኩ አደጋውን ለመቀነስ አስተዋጽዖ አበርክቷል።
ይሁንና ህብረተሰቡ በእነዚህ አካላት ከመኪና አደጋ ራስህን ጠብቅ ወይም ደግሞ ግራ መስመርህን ይዘህ ተጓዝ ስለተባለ ብቻ ከአደጋው ከመዳን ንብረትም ከመውደም አልቀረም፡፡ ይልቁንም መሰልጠን ያለባቸውን በማሰልጠን በተለያዩ መንገዶች የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ማግኘት ሳይገባቸው የሚያገኙ ሰዎችን መከላከል ሳንችል አደጋውን እንቀንሳለን ማለት ዘበት ነው፡፡ መጀመሪያ ይህን የተበላሸ አካሄድ ማረም ያስፈልጋል።
ሰዎች ይህን ትልቅ ጉዳይ ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው፡፡ መንግስትም በራሱ በኩል መውሰድ ያለበትን እርምጃ ይወስዳል፤ ምንም ጥያቄ የለውም ፤ ለዚህም ዝግጅት እየተደገ ነው። መንግስት ስራው በቂ ነው ብሎ አያምንም።
አዲስ ዘመን፡- የመንገድ ትራፊክ አደጋን ለመከላከል የብዙ አካላት ሚና ወሳኝ ነውና ቅንጅታዊ አሰራሩ ምን ይመስላል?
አቶ ደረጀ፡- ይህ ምንም ጥያቄ የለውም፤ ብዙ ክፍተቶች አሉበት፤ አንዳንዱ መንገድ ግንባታው ተጠናቅቆ ለትራፊክ ክፍት ቢሆንም አስፈላጊው የመንገድ ዳር ምልክት አልተሟላለትም።
በነገራችን ላይ የእኛ አገር መንገዶች ዲዛይን ሲደረጉ የትራፊክ አደጋን ከግንዛቤ ያስገቡ አይደሉም። ከተሰሩም በኋላ በተደጋጋሚ አደጋ እየተከሰተባቸው የእርምት እርምጃ አይወሰድም። ምልክቶች ሳይተከሉ መንገዶች ለትራፊክ ክፍት መሆናቸው ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ ተተክለውም በተለያየ ምክንያት ሲጠፉ በምትካቸው ሌላ የማይተከልበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ በመሆኑም ተቀናጅቶ በመስራት በኩል ብዙ ስራዎች ይቀራሉ፡፡
አዲስ ዘመን ፡- የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ህብረተሰቡና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቀጣይ ምን ማድረግ አለባቸው ይላሉ፡፡
አቶ ደረጀ፡- የመንገድ ትራፊክ አደጋ ከሚነገረውም በላይ በጣም እየጎዳን ነው። ይህን እውነታ ሁላችንም ልንገነዘበው ይገባል። አንዳንዶቹ አደጋዎች በፍጹም ሰው ሊሞትባቸው ንብረት ሊጠፋባቸው በማይገባ መልኩ ግለሰቦች በሚፈጽሙት የሌብነት ተግባር የሚከሰቱ ናቸው። በመሆኑም በግልም በመንግስትም ሃላፊነቱ የተሰጠን አካላት ቆም ብለን ማሰብ ይኖርብናል።
ህዝቡም የማሽከርከር ብቃት ማረጋገጫ ለመውሰድ ሲቀርብ ተገቢውን ስልጠና መውሰድ እንዳለበት ማወቅ ያስፈልጋል፤ ቤተሰብም ልጆቹ በትክክለኛው መንገድ ማለፋቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ደረጀ:- እኔም በጣም አመሰግናለሁ፡፡

እፀገነት አክሊሉ

Published in ኢኮኖሚ

ከጆሴፍ ስታሊን በመቀጠል በሩሲያ ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳደሩ መሪ መሆናቸው የሚነገርላቸው የ65 ዓመቱ ቭላድሚር ፑቲን ለሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት አገራቸውን በፕሬዚዳንትነት ለማገልገል ቃለ መሃላ ፈፀሙ።
ሩስያን በፕሬዚዳንትነትና በጠቅላይ ሚኒስትርነት እኤአ ከ1999 ጀምሮ የመሩት ፑቲን ከሁለት ወራት በፊት በተካሄደው አገራዊ ምርጫ አስቀድሞ እንደሚያሸንፉ በተገመተው መሰረት ከ76 በመቶ በላይ ድምፅ በማግኘት ማሸነፋቸው ይታወሳል።
ለአራተኛ ጊዜ በፕሬዚዳንትነት ለማገልገል የበቁት ቭላድሚር ፑቲን በቀጣይ ስድስት ዓመታት የስልጣን ቆይታቸውም አገራቸውን በታማኝነት ለማገልገል የህዝባቸውን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት ለማስጠበቅ ብሎም የአገራቸውን ሉአላዊነት ለማስከበር በህዝብ ፊት ቃል ገብተዋል።
ፑቲን ከአምስት ሺ በላይ ታዳሚያን በተገኙበት የክሪሚሉ አዳራሽ በተካሔደ የቃለ መሃላ ስነ ስርዓት ላይ ቀጣዮቹ ስድስት ዓመታት አገራቸው በዓለም ዓቀፍ መድረክ ጠንካራ ፈርጣማ ጡንቻዋን የምታሳይበት፤ ወታደራዊ ሃይሏን ይበልጥ የምታጠናክርበትና ለህዝቦቿ ሁለንተናዊ ለውጥ የምትታትርበት እንደሚሆን አስታውቀዋል። የቀድሞዋን ሃያል ሩሲያ ዳግም እውን ለማድረግም የእርሳቸው ሃላፊነት ጎልቶ እንደሚንፀባርቅ አረጋግጠዋል።
«የህይወቴ ዋነኛ ዓላማና ተግባሬም አባት አገሬና ህዝቤን በቁርጥነት ማገልገል ነው»ሲሉም ተደምጠዋል።
ቃለ መሃላውን ተክትሎም የበርካታ ወገኖች ጥያቄና የትኩረት አቅጣጫ የወሰደው ፕሬዚዳንቱ በጠቅላይ ሚነስትርነት ማንን ይሾማሉ የሚለው ሲሆን፤ የምንጊዜም ታማኝ ባልደረባቸው ዲሜትሬ ሜድቬዴቭን በቦታው እንዲቀጥሉ ማድረጋቸው እንደማይቀር ተገምቷል።
አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሾሙ ከሆነም አገሪቱ አዲስ የፖሊሲ አቅጣጫን የመከተል ዝንባሌ ሊኖራት እንደሚችል የተገመተ ሲሆን፣ ከዚህም በላይ ምናልባትም ሰውየው ምትካቸው እንዲሆኑ የፈለጉት ሰው ስለመሆኑ ፍንጭ መሰጠቱም ተጠቁሟል ።
አሜሪካ በአገሪቱ ላይ የጣለችው ማዕቀብ፤ ዓመታትን የተሻገረና ማቆሚያው የማይታወቀው የሶሪያ ጦርነት የቀድሞው የ66 ዓመቱ የሩሲያ ሰላይ ሰርጌ ስክሪፓል ከ33 ዓመት ሴት ልጃቸው ሁሊያ ጋር የመመረዛቸው ክስተትና መሰል ቀውሶች አፋጣኝ እልባት ማጣታቸውን ትከትሎ አንዳንድ ዲፕሎማቶች ስለመጪው እጅጉ እንዲጨነቁ አስገድዷቸዋል።
አንዳንዶች በአንፃሩ የፑቲን ቀጣይ ዓመታት አገሪቱ ከምዕራባውያን ጋር ያላትን የሻከረ ግንኙነት እሰጣገባና ግትር አቋም የምታለሳልስበት እንደሚሆን ተስፋ አድርገዋል።
ፑቲን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የአገራቸውን ሃያልነት በማስጠበቅ ረገድ በአገሬው ህዝብ ዘንድ ተወዳጅነት ያላቸውን ያህል በዋሽንግተን መንግስት ቀማሪነት የተጣለው ማዕቀብ፤ የአገሪቱ ኢኮኖሚና የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ እያደር መቀነስ፣ የነዳጅ ዋጋ ዝቅ ማለትና ግሽበቶች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በፑቲን ላይ ፊታቸውን የሚያጠቁሩባቸው እንዲፈጠሩ ምክንያት መሆን ጀምሯል።
ከቀናት በፊትም በተለይ በአስተዳደራቸው ላይ ተቃውሞ የሚያሰሙ ሰልፈኞች ከፖሊስ ጋር ግጭት ፈጥረዋል። ከአንድ ሺ በላይ የሚሆኑትም በዚህ ተግባራቸው ምክንያት ለእስር ተዳርገዋል። ከእነዚህ መካካል አንዱም በፕሬዚዳንታዊ የምርጫ የፑቲን ዋነኛ ተፎካካሪ ሚሊየነሩ ኮምዩኒስት ፓቬል ገሩዲኒን እንደሚገኙበት ተመላክቷል።
በመሰል ተቃውሞና ድጋፎች የታጀበው የፕሬዚዳንቱ ቀጣይ ስድስት ዓመታት የጎዞ ምዕራፍ ጅማሮም በቀጣይ በርካታ ፖለቲካና ማህበራዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎችን መመለስ እንደሚጠበቅባት የብዙዎች እምነት ሆኗል። ከፕሬዚዳንቱ አገራዊ የቤት ስራዎች ግንባር ቀደም ሆነዋል።
በቀጣይ ስድስት ዓመታት ሞስኮን በበላይነት የሚመሩት ቭላድሚር ፑቲን እኤአ በ2024 ሁለተኛውን የምርጫ ዘመናቸውን ሲያጠናቅቁ 71 ዓመት ይሆናቸዋል። ዘገባው የሮይተርስና የቢቢሲ ነው።

 

የ«አሚሶም»የሶማሊያ ተልዕኮ ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገዋል ተባለ

 

የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ተልዕኮ (አሚሶም) ሰላም አስከባሪ ሃይል በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ቀስ በቀስ ሚናውን አስርክቦ ከሶማሊያ እንዲወጣ ማድረግ እጅግ አደገኛ ውጤት እንደሚኖረው ተገለፀ።
የተልዕኮ ሴክተር አንድ ሃላፊ ኡጋንዳዊው ኮማንደር ብርጋዴል ጄኔራል ፖል ሎኬክ ዋቢ በማድረግ አፍሪካ ኒውስ እንደዘገበው ሰላም አስከባሪ ሃይሉን ለማስወጣት መሞከር አልሻባብን በመደምሰ በሶማሊያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በሚደረገው ጥረት ላይ ከፍተኛ ኪሳራን የሚያስከትል ነው።
«ሶማሊያ በራሷ አቅም የህዝቡን ሰላም ማስጠበቅ አትችልም፤ ወታደራዊ ሃይሉ ሶማሊያን ለቆ የሚወጣበት ትክክለኛው ሰዓት አሁን አይደለም፣ በተለይ የአገሪቱን የፀጥታ ሃይል በማጠናከር ረገድ ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገናልም» ብለዋል።

አሚሶም በሶማሊያ ሰላም ማስከበር ከተሰማራ አስራ አንድ ዓመታት አስቆጥሯል


ሶማሊያ በራሷ አቅም የህዝቡን ሰላም ማስጠበቅ እንድትችል ለማድረግም ተልዕኮው በአሁኑ ወቅት ለበርካታ የአገሬው የፀጥታ ሃይል አባላት ስልጠና በመስጠት ላይ መሆኑን የገለፁት ብርጋዴል ጄኔራል ፖል ሎኬክ፤ ይህን ተግባር ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ደግሞ የተወሰነ ጊዜ መጠየቁ የግድ መሆኑን አልሻባብም ቢሆን እጅጉን ተዳከመ እንጂ ፈፅሞ አለመሞቱን አብራርተዋል።
የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አሜሶም በሶማሊያ ያሰማራቸውን ሰላም አስከባሪ ሃይሎች ቁጥር እንዲቀንስ ጥያቄ ማቅረብ መጀመሩን ያስታወሰው ዘገባው፣ በዚህ ጥያቄ መሰረትም አንድ ሺ የሚሆኑት ሰላም አስከባሪ ወታደሮች መቀነሳቸውንና ወደ መጡበት እንዲመለሱ መደረጉን አመላክቷል።
በአሁን ወቅት በአሚሶም የሶማሊያ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ከሚሳተፉ 21 ሺ ወታደሮች መካከልም በዚሁ የፈረንጆች ዓመት ጥቅምት ወር ተመሳሳይ የቅነሳ እቅዶች ለመከወን መታቀዱን አስታውቋል።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አሚሶም በ2021 በሶማሊያ ያለውን የሰላም ማስከበር ተልዕኮ አጠናቆ ተግባሩን ለአገሬው መንግስት እንዲያስረክብ ጠይቋል። ይህ የድርጅቱ እቅድም የአፍሪካ ህብረት የሰላምና የደህንነት ምክር ቤት እንደተቀበለው በዘገባው ተመላክቷል።
የኅብረቱ ጦር ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ማለትም ከዩጋንዳ፤ ኢትዮጵያ፤ ኬኒያ፤ ብሩንዲ፤ ከሶማሊያ፤ ከጅቡቲ እንዲሁም ከሴራሊዮን የተወጣጡ ናቸው። የአሜሶም አልሻባብን የማስወገድና የሶማሊያ ሰላም በማስከበር ዘላቂ ሰላም የማረጋጋጥ ተግባር አስራ አንድ ዓመታትን አስቆጥሯል።

ታምራት ተስፋዬ

 

Published in ዓለም አቀፍ
Tuesday, 08 May 2018 16:41

የሠራተኛው ቀን ሲታሰብ

ባለፈው የሚያዝያ ወር በአገራችን ካከበርናቸው በዓላት መካከል «ሚያዝያ 23 የተከበረው ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን ፣ ሚያዝያ 27 የተከበረው የጀግኖች አርበኞች የድል መታሰቢያ እና ሚያዝያ 25 የተከበረው የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ይገኙበታል። የሠራተኞች ቀን በዋናነት በሠራተኛ ሰዎች መብት መጠበቅና መከበር ላይ ያተኮረ ነው። ሁሉም ነገር የሚሠራው ለሰዎች በሰዎች ነው። ብለው ከዚህ ውጪ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ የለም። አዋጆች ፣ መመሪያዎች፣ ደንቦች፣ የሥራ ውሎች ሁሉ ከመቶ ዓመታት በላይ ሠራተኞች ሲታገሉላቸው እየወደቁ እየተነሱ በዓለም ደረጃ እየተሻሻሉ የመጡ ግን ዛሬም ድረስ ብዙ ችግር ያሉባቸው ሂደቶች ናቸው። በየአገሩ በሠራተኞች መብት አጠባበቅ ዙሪያ ብዙ የተሻሻሉ ነገሮች መኖራቸው ባይካድም እያደገ የመጣው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበረሰባዊና ፖለቲካዊ ለውጥ ያመጣቸው ችግሮች አሉ። የሠራተኞች መብት አለመከበር ከሰብዓዊ መብቶችና መፍትሔ ካጣው ስደት ውስብስብነት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። ሁሉም የሥራ ዘርፎች ውስጥ ጐጂ አሠራሮች አሉ። አንድ ምስክርነት እንስማ። አቶ አስናቀ በኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበር ኮንፌዴሬሽን ውስጥ የታወቁ የህግ ባለሙያና ኃላፊ ናቸው። ከአንድ ኤፍ ኤም ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ከተናገሯቸው ቁምነገሮች መካከል የሚከተለው ይገኝበታል። «ልጅቱ በአንድ የአበባ ምርት ዘርፍ በተሰማራ ኩባንያ ውስጥ የምትሠራ ተቀጣሪ ናት። ቢሯቸው ለአቤቱታ ሄደች። ታሪኳን ስትናገር ታለቅሳለች። በኋላ ሰውየው «ምን ያስለቅስሻል አስጨነቅሺኝ እኮ--- ለቅሶውን አቁሚና በደልሽን ንገሪኝ» አላት። እሷም ስትመልስ «እኔኮ እያለቀስኩ አይደለም። በምሠራበት የአበባ ሥራ የምንጠቀምበት ኬሚካል ዓይኔን ስለጐዳኝ እንባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም።» አለች በጣም የሚያሳዝን ነው። ለሠራተኞች ደህንነት አይታሰብም ማለት ኬሚካሉ በጤና ላይ ስለሚያስከትለው ጉዳት መረጃ የለም ማለት ነው? መከላከያ /ጭምብል/ የለም ማለት ነው? ከተጐዳሽ በኋላ የህክምና ወጪና ካሣ የምታገኝበት መንገድ /ውል/ የለም ማለት ነው? ይህች ሠራተኛ ቀሪ ዕድሜዋን እንዳለቀሰች ትኖራለች ማለት ነው ? ይህ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት አይደለምን? ሰብዓዊ መብት ማለት እኮ በህይወት የመኖር መብትና ከአካል ጉዳት የመጠበቅ መብት ነው። በሥራቸው ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሠራተኞች የወደፊት ሁኔታ ምንድንነው? የሰው ልጅ ህይወት ትልቅ ዋጋ አለው። የሰው ልጅ ሰብዓዊ ክብር መጠበቅ አለበት የልማት ዴሞክራሲ ዕድገት የሃገር መሰረቱ የሰው በሰውነቱ መከበር ነው። ከፖለቲካ ጋር ከተያያዙ የመብት ጥሰቶች የበለጠ ትኩረት ማግኘት ያለባቸው በማህበራዊ ህይወት ውስጥ እየተፈጸሙ ያሉ የመብት ጥሰቶች ናቸው። አካላዊና ስለልቦናዊ ጥሰት እየተፈጸመበት ያለን ሠራተኛ ሰብዓዊ መብቱ ተከብሮለታል የምንልበት ምን አፍ አለን። ይህ እንግዲህ የሠራተኛው መብት አለመከበር ከአጠቃላዩ የሰብዓዊ መብት መከበር ጋር ያለውን ቁርኝት የሚያሳይ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ በእህታችን ምሳሌነት የምንረዳው «እሷን ያዩ» ሌሎች ሰዎች እንዴት ሥራ ፍለጋ ወደ ኩባንያዎች ይሄዳሉ። ምን መጣብን ብለው ይሄዳሉ በጉልበቴ ሠርቼ ራሴንና ቤተሰቤን አስተዳድራለሁ ብለው ሲቀጠሩ ጥንቃቄ የማይደረግላቸው ከሆነ ዓይናቸው የሚጠፋ ከሆነ አካላቸው ጐድሎ ህይወታቸውን የሚያጡ ከሆነ «ሥራ» የሚባለው ነገር ምን ይጠቅማቸዋል። ስለዚህ ያላቸው አማራጭ አንድ ብቻ ይሆናል። ስደት፣ ስደት ደግሞ የራሱ ጣጣ አለው። ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ጉልበት ያገኛል። በየማቋረጫው የሚወጡትን ዜጎች ትተን በቦሌ አየር ማረፊያ ብቻ በቱሪስት ቪዛ የሚወጡ ዜጐች ቁጥር በየቀኑ ከአንድ ሺህ በላይ ነው።
የቱሪስት ቪዛ ለጉብኝት ብቻ የሚያገለ ግል ከአንድ እስከ 3 ወር የሚደርስ ዕድሜ ብቻ ያለው ፈቃድ ነው። ይህን ፈቃድ ይዘው ሲሄዱ ህገወጥ ደላሎች መዳፍ ላይ ይወድቃሉ። ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑና መውጣት መሥራት የማይፈቀድላቸው በትምህርታቸው 8ኛ ክፍል ያልደረሱ ለሥራ የሚሆናቸው ክህሎትና ስልጠና የሌላቸው የብቃት ማረጋገጫ ያልተሰጣቸው ዜጐች በቱሪስት ቪዛ እየወጡና ለጉዳት እየተዳረጉ ነው።
ይህን ከአገር ውጪ የሚደርስ ጉዳት ለማስቀረት የሚቻለው እዚህ አገር ውስጥ ያለውን የሠራተኛ መብት ማስከበር፣ ደህንነቱን መጠበቅ፣ ለደረሰበት ጉዳይ ካሣ መስጠት ፣ተመጣጣኝ ክፍያ /ደመወዝ/ እንዲያገኙ በማስቻል ነው። አንዳንድ ኩባንያዎች በተለይ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችም ለጭንቅላት (ራስ) መከላከያ የሚሆን ሄልሜት እንኳ የማያቀርቡ አሉ። ለመወጣጫ ተብሎ በየሕንፃው ላይ የተሰደሩ እንጨቶችና የሚጠቀሙባቸው የሸክላ ጡቦች ደረጃቸውን ያልጠበቁ በመሆናቸው ለአደጋ የሚያጋልጡ ናቸው። በአሁኑ ጊዜ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚደርሰው አደጋ በመንገዶቻችን ላይ ከሚደርሰው የትራፊክ አደጋ አይተናነስም።
ኮንስትራክሽን ሲባል ሕንፃ፣ የመንገድ፣ የኃይል ማመንጫ ፣ የውሃ ግድብና ቁፋሮ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የባብር ሃዲድ ወይም ሌላ የሲቪል ምህንድስና ሥራዎች ማስገንባትና መገንባትን ሁሉ ይጨምራል። በእነዚህ ሥራዎች የሚሳተፉ ብዙ ተቋማት ግለሰቦች አሉ። የሥራው ባለቤት አለ የሥራው ተቋራጮችና አማካሪ መሐንዲሶች አሉ። በውስጣቸውም ብዙ የውል ዓይነቶች አሉ። የስኬት ውል የዲዛይንና ግንባታ ውል የሚባሉ የእያንዳንዱን ሥራ በኃላፊነት ወስዶ መሥራት የሚያስችሉ ውሎች ናቸው። የሠራተኛ ጉዳዮችን በሚመለከት የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ አለ። ስልጠናና ሴሚናርም ተሰጥቶበታል። አዋጅ በባህርይ ከተለዋዋጭ ሁኔታዎች ማለትም ከቴክኖሎጂ ዕድገት፣ ከኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ከተለያዩ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ካሉ የጋራዊና ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር በየጊዜው እየተገናዘበና እየተፈተሸ ሊጣጣም የሚገባው ጉዳይ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዳኞች በሶደሬ በተካሄደው ሴሚናር ላይ «በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/1996 የተካተቱ ለውጦች» በሚል ርዕስ የቀረበውን መግለጫ መመልከት ይቻላል።
በኮንስትራክሽን ውሎችና በዋስትና መብት ላይ «የኮንስትራክሽን ውሎች መሠረታዊ ባህርያት» እና «የዋስትና መብት አጠባበቅ በኢትዮጵያ የወንጀል ህግ አንፃር» በሚል ርዕስ የተዘጋጁና ጠበቆች፣ ዳኞች ዐቃቢያነ ህግ እና ሌሎች ባለሙያዎች የተሳተፉበት ሴሚናር ጥቅምት 20 ቀን 1997 በሆቴል ዲ አፍሪክ የተካሄደውን መጥቀስ ይቻላል። ከዚህ በኋላም በኮንስትራክሽን ጉዳዮች የተለያዩ ሴሚናሮች፣ ስልጠናዎች፣ ማሻሻሎች ተደርገዋል። መሻሻል የሚገባቸው አዋጆች የሉም ማለት ባይሆንም በአብዛኛው የህግ ችግር የለብንም ያሉት ህጐች ሊያሠሩን ይችላሉ። ችግራችን አፈፃፀም ላይ ነው። ተሠርተው ያልተጠናቀቁ ሕንፃዎች በኪራይ የሚተላለፉበት ሁኔታ ነው ያለው። ባንኮች ባላለቀ ሕንፃ ውስጥ ለደምበኞች አገልግሎት መስጠታቸው ሲገርመን ጭራሽ የሕፃናት ትምህርት ቤት ተሠርቶ ባላበቃ ሕንፃ ሥር የሚያስተምሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል። የሰሞኑ መነጋገሪያም ይሄው ነበር። የግንባታ ግብአት የሆኑ ብረታ ብረቶች ሸክላ፣ ጠጠር፣ አሸዋ፣ እንጨት... ወዘተ ባለመኪናና እግረኞች መተላለፊያ እስኪያጡ ድረስ መንገድ የሚዘጉበት ሁኔታ መኖሩ ይታወቃል።
የሠራተኞችን መብትና ዋስትና በተመለከተ በኢንቨስተሮች አማካይነት ያለው ሁኔታም ይሄን ያህል የሚጨበጨብለት አይደለም። ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ሲባል «ርካሽ ጉልበት» አለን ብሎ መስበክ አያዋጣም። ባለቤት ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀለውም እንደሚባለው እኛ ርካሽ ነው ያልነውን የዜጐች ጉልበት ኢንቨስተሩ በወድ ወይም በተመጣጣኝ ዋጋ ሊገዛን አይችልም። የሥራ ዕድል ማግኘቱ አንድ ነገር ሆኖ ሠራተኞች ተመጣጣኝ ክፍያ አግኝተው ህይወታቸውን እንዲለውጡ ማስቻል ደግሞ ዋና ጉዳይ ነው። ኢንቨስተሩ የሚመጣው ትርፍ ለማግኘት ነው። ትርፍ የሚገኘው ከሠራተኛ ጉልበት ነው። ለዚህ ጉልበት ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ መሥራት አለበን። ሌላው ችግራችን «የእውቀት ሽግግር» የሚባለው ነው። ዓላማው ዜጐቻችንን ከኢንቨስተሮች ጋር አብረው በመሥራት እውቀት ይቀስማሉ። አገሪቱ በቀጣይ በምትሠራቸው የልማት ሥራዎችም የላቀ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ራሳቸውን አሻሽለው የሥራቸው ጌታ ይሆናሉ። በሚል እሳቤ ነው። ነገር ግን እየሆነ ያለው በእርግጥ እንዲህ ነው ወይ? አንዳንድ ኩባንያዎች አገር በቀል የሆኑት እንደ ሜቴክ የመሳሰሉ ድርጅቶችን በሚያንቀሳቅሱበት የልማት ዘርፍ የአካባቢውን ዜጐች አስተምረውና አሠልጥነው በግንባታ መሳሪያዎች (earth moving machines) ባለሞያ አድርገው ዶዘርና ግሬደር ሲያንቀሳቅሱ አይተናል። የውጭ ኢንቨስተሮች አንዳንዶቹ ግን ግቢያቸውን እንኳን ለማስጐብኘት ፈቃደኛ አይሆኑም።
ዋናው ነገር የሠራተኞችን ቀን ስናስብ ስለቀኑ ሳይሆን ስለሰብዓዊ ፍጡሩ ሠራተኛ መሆን አለበት። ሠራተኛውን በሀገሪቱ ልማት ተሳታፊ ማድረግ ብቻውን በቂ አይደለም። ከልማቱም ተጠቃሚ መሆን አለበት። በህግ የተደነገጉ መብቶች መሬት ወርደው ሊከበሩለት ይገባል። የህግ የበላይነት ይበልጥ መረጋገጥ አለበት። አሠሪዎች እንደፈለጉ የሚያንገላቱት ሊሆን አይገባም። የሠራበትን ደመወዝ በውሉ መሠረት በወቅቱ ማግኘት አለበት። እስከ ሦስት ወር ያህል ደመወዝ የማይከፈላቸው ሠራተኞች አሉ። ያቺን ከእጅ ወደአፍ የሆነች የጉልበቱን ዋጋ በተገቢው ጊዜ መቀበል መቻል አለበት። እንደራሳችን እንየው ከሠራተኛው ጋር ያለን ግንኙነት ግልጽ መሆን አለበት። ግዴታውን ብቻ ሳይሆን መብቱንም ማወቅ አለበት።
የሠራተኞች ቀን ሲታሰብ አብሮ ብቻ ሳይሆን ቅድሚያ ተሰጥቶት መታሰብ ያለበት የሠራተኛ ሴቶች መብት ተጠቃሚነት ነው። በተለይ በኮንስትራክሽንና በቤት ሠራተኝነት ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶችን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ አሠራር መመርመርና ማጠናከር ያስፈልጋል። በዚህ ዘርፍ ያሉ ሴቶች ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚቻል መጠነ መፃፍና ማንበብ የማይችሉ በመሆናቸው አሠሪው በነገራቸው ሁሉ የሚስማሙ ናቸው። እነሱ ተስማሙ ማለት መብታቸው ተከበረ ማለት አይደለም። ብዙዎቹ ሴቶችም ሠርተው ያገኟትን ገንዘብ አጠራቅመው የመጀመሪያ ምኞታቸው ፓስፖርት ማውጣት ነው። ከዚያ በኋላ ልባቸው ወደ ውጭ ነው። የውጭ አገር ሥራ ፍለጋ በህገወጥ ደላላ እጅ መንገላታት ነው። ሲመለሱም ጤናቸውን አጥተው የሠሩበትን ገንዘብም ተነጥቀው ባዶ እጃቸውን ነው እነዚህን ሴቶች የዘርፉ ህግ ሊታደጋቸው ይገባል። ወደ ውጭ ማየት የሚጀምረው የውስጡ አልመች ሲል ነው። ውስጣችንን ለሠራተኛ ሴቶች አመቺ እናድርግ!!!!

ግርማ ለማ

Published in አጀንዳ

ሀገራችን ድህነትን ለመቀነስ፣ኢኮኖሚዋን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር፣ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለመሰለፍ ወዘተ ራእይ ሰንቃ ለተግባራዊነቱ ርብርብ ማድረጓን ተያይዛዋለች፡፡ይህን እውን ለማድረግም የተለያዩ ዘርፎችን የሚመለከቱ ፖሊሲዎች ፣ስትራቴጂዎች፣ ግቦች መመሪያዎች ደንቦች አዋጆች ወጥተው ሥራ ላይ እንዲውሉ ተደርጓል። ሀገራዊ እቅዶች ወጥተውም ሥራ ላይ ውለዋል፡፡
ሀገሪቱ ይህን ሁሉ ለማከናወን ስትነሳ የአቅም ክፍተት መኖሩን ታሳቢ በማድረግም ለአቅም ግንባታ ተግባር ትኩረት ሰጥታለች፡፡ በሀገሪቱ የሠለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ያስቻሉ በርካታ የአቅም ግንባታ መርሐ ግብሮች ተካሂደዋል፡፡ በዚህም በእያንዳንዱም ተቋም ውጤታማ የአሠራር ስርዓት እንዲኖር ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ በሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች የተመዘገበው ዕድገትና ለውጥም የዚሁ ጥረት መገለጫም ነው ማለት ይቻላል፡፡
ከዚህ አንጻር በተለያዩ ዘርፎች የሚሰጠው ስልጠና እንዳለ ሆኖ የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስትቲዩት ተቋማዊ የማስፈጸም አቅምን ለማጎልበት የሚያስችሉ የተለያዩ ሥልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ተቋሙ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል አንዱና ግንባር ቀደሙም የሥራ አመራር ስልጠና መስጠት ሲሆን፣ በዚህም ወደ 47 ሺ 849 ሠልጣኞችን በማሠልጠን ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ ሥልጠናዎቹ የተቋማትን የማስፈፀም አቅም በማጎልበት ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት መስጠት የሚችሉበትን ሁኔታ ፈጥሯል፡፡
እንደሚታወቀው ስልጠና ኃላፊነትን በአግባቡና በተገቢው መንገድ ለመወጣት ያግዛል፡፡ የሠለጠነ የሰው ኃይል ያላቸው ተቋማት የተቋማቸውን ርዕይና ተልዕኮ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ማሳካት እንደሚችሉም ይታመናል፡፡ በሚሰጧቸውም አገልግሎት ከደንበኞቻቸው ቅሬታ እንዳይነሳ የሚጠበቅባቸውን ተግባር ያከናውናሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡ በዓለማችን ያሉ የበለጸጉ አገራትን መለስ ብለን ስንቃኝም ለማደጋቸው ትልቁ ምክንያት ለሰው ሀብት ልማታቸው የሰጡት ትኩረት ነው፡፡
የኢፌዴሪ መንግሥትም እያደረገ ባለው የሠለጠነ የሰው ሀብት የማልማት ሂደቱ ረጅም ርቀት የተጓዘ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም ውጤት በመታየት ላይ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት መረጃ እንደሚያመለክተውም፤ ኢንስቲትዩቱ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት የተሰጡትን የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች የገመገመ ሲሆን፣ እነዚህም ሥልጠናዎች የመንግሥትንም ሆነ የህዝቡን አቅም የተሻለ እንዲሆን ማድረጋቸውን ለማወቅ ተችሏል። በአገራችን እየተመዘገበ ላለው ልማትም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በተለያዩ መርሐ ግብሮች የተሰጡ ሥልጠናዎች አቅምን በማጎልበቱ በኩል ትልቁን ሚና መጫወት ችለዋል፡፡
የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎቹ በእያንዳንዱ ተቋም ውስጥም ሲፈተሹ የማይናቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ይታወቃል፡፡ በተለይም ሠልጣኞች የተቋማቱን ደንበኞች በተገቢው መንገድ የማገልገል ተነሳሽነታቸው እንዲጨምርና የግለሰብ ፈፃሚዎች አፈፃፀምም እንዲሻሻል ማድረጋቸውን ኢንስቲትዩቱ ካካሄደው ጥናት ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
አዳዲስ አሠራሮችን ለመተግበር ፣ የሠራተኞችና አመራሮችን አቅም ለማጎልበት ሥልጠና መስጠት የግድ ነው። የሀገሪቱን ዕድገት የማስቀጠሉም ሥራ እንዲሁ ከአቅም ግንባታ ውጪ አይታሰብም። ለዚህም በሥልጠና ላይ የታየውን ውስንነት ለማስወገድ ሥራ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡
ሥልጠና በሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች ለተመዘገበው ዕድገትም የራሱን ሚና የተጫወተ ቢሆንም ፣ሥልጠናዎች የሚፈጥሩትን አቅም በአግባቡ ካለመረዳት የተነሳ በተለያዩ ተቋማት በሥልጠና ሂደቱ ላይ የተለያዩ ክፍተቶች ተስተውለዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ተቋማት የሚያስፈልጋቸውን የሥልጠና ርዕስ በጥናት ላይ ተመስርተው አለመምረጣቸውና ሥልጠናዎችን አቅዶ በመስጠት በኩልም የትኩረት ማነስ ይታያል፡፡
አንዳንድ ተቋማት ሥልጠናዎችን እንደ መዝናኛ አድርገው ሲቆጥሩም ታይቷል፡፡ ሠራተኞች በሥራ ገበታቸው ከሚያጋጥማቸው ተከታታይ የሥራ ጫና እፎይታ የሚያገኙበት አድርገው እየቆጠሩም ይገኛሉ፡፡ በእዚህ ዓይነት መልኩ ለሥልጠና የሚላኩ ሠራተኞች ‹ዘና›› ማለትን እንጂ የአቅም ግንባታ ሥልጠናውን ከቁብ አይቆጥሩትም፡፡ ይህ አካሄድ በራሱ የአመለካከት ችግር በመሆኑ ተቋማት ለሥልጠና የሚልኳቸው ሠልጣኞች ተገቢ ሠልጠኞች መሆናቸውን ማረጋገጥና የሄዱበትን ዓላማ ያሳኩ ስለመሆናቸው መፈተሸ ይጠበቅባቸል፡፡ ተቋማት ተገቢውን ሠልጣኝ በመመደብ ለተቋሙ ውጤታማነት የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ሥልጠናዎች የፐብሊክ ሰርቪሱን ተጨባጭ ችግሮች በመለየት ውጤታማ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚያስችሉ መሆናቸው ታምኖበት ለሥልጠና የሚመለመሉ አካላትም በእኔነት ስሜት ሊሳተፉ ይገባል፡፡ ተቋማት ለሥልጠና የላኳቸው አካላት ሥልጠናውን በአግባቡ እየተከታተሉ ስለመሆናቸው ተገቢውን ቁጥጥር ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ የድህረ ሥልጠና ክትትል ስርዓት መዘርጋትም ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ሠልጣኞች ስለወሰዱት ሥልጠና ሪፖርት እንዲያቀርቡ ከማድረግም በተጨማሪ በሥራ ላይ እንዲተገብሩት ማድረግም ይገባል። ተቋማት ይህን በማድረግ ሥልጠናው ሠራተኛውን እና ተቋሙን እንዲለውጥ ማስቻል አለባቸው ፡፡
ተቋማት የሚያሠለጥኗቸው ሠልጣኞች የተሻለ አቅም እንዲያጎለብቱና በመንግሥት የተያዘው እቅድ ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆን በዋናነት ሥልጠናውን የሚሰጠው ኢንስቲትዩት በቂ ዕውቀትና ክህሎት ያለው ባለሙያ ሊኖረውም የግድ ነው፡፡ ማሠልጠን ብቻ ሳይሆን ሠልጣኞቹ የሚመለከታቸው አካላት ስለመሆናቸውም ማረጋገጥ ከተቋሙ ይጠበቃል፡፡ አገርን የማሳደግና ተቋምን የማሻሻል ሂደት በአንድ ጀምበር መምጣት እንደማይችል ሁሉ የሠራተኞችን አቅም ለማጎልበት ታስበው የሚሰጡ ሥልጠናዎች ተከታታይ መሆንም ይኖርባቸዋል፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ በጅቡቲና በሱዳን ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት የሀገሮቹን ወደቦች በጋራ በማልማትና በማስተዳደር ኢትዮጵያ ተጠቃሚ የምትሆንበት ስምምነቶች ላይ መደረሱን የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ማመልከታቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ስምምነት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያስገኘውን ፋይዳ በተመለከተ ምሁራን ምን ይላሉ?

የአፍሪካ ቀንድ ተመራማሪው ዶክተር በለጠ በላቸው አንድ አገር የራሷ ወደብ ከሌላት በርካታ ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች እንደሚገጥሟት በመጥቀስ፣የወደብ አማራጮች ሲበራከቱ የጠቃሚነቱ መጠንም በዛው ልክ ከፍ እያለ እንደሚሄድ ያብራራሉ። የወጪና ገቢ ንግዷን በጅቡቲ ወደብ ብቻ እያሳለጠች የምትገኘው ኢትዮጵያም ይህንን ከግምት በማስገባት አማራጭ ወደቦች እንዲኖራት ለማድረግ የሚያስችሉ ጥረቶችን ስታደርግ መቆየቷን ይጠቅሳሉ።
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታቸው ዘሩ አገሪቱ ወደብ ተከራይታ እየተጠቀመች መሆኗን ጠቅሰው፣ በቀጣይም ተከራይታ መጠቀም ትችል ይሆናል ይላሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ እያደገ ያለውን የወጪና ገቢ ንግድ እንዲሁም የህዝቡንና የውጭ ባለሀብቱን ፍላጎት ማርካት ግን እንደማትችል ያመለክታሉ። እነዚህን ወደቦች በተገኘው አማራጭ ሁሉ መጠቀም እንደሚገባም ጠቅሰው፣አብሮ ማልማቱና ማስተዳደሩ ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርግና ስትራቴጂካዊም መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ ወደብን በጋራ የማልማትና የማስተዳደር ጉዳይ ሊበረታታ የሚገባውና አገሪቱ አሁን ያለችበትን ሁኔታ ከግምት ያስገባ መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡
የመከራየት ሃሳቡን በመተው ከጅቡቲና ከሱዳን ጋር ብቻ ሳይሆን የበርበራና የኬንያውን ላሙ ወደብንም በጋራ አልምቶ ለመጠቀም የኢትዮጵያ መንግሥት በትኩረት መስራት እንዳለበትም ይናገራሉ፡፡
አቶ ካህሳይ ወልደእየሱስ፤‹‹ወደብ መከራየት ጥገኝነት ከመሆኑም በላይ ወጪው ይበዛል፤ይህ በመሆኑም ዕድገት ይቀጭጫልም፤ ይገደባልም፡፡ የሚፈለገውን ያህል ለመሮጥም አያስችልም›› ይላሉ፡፡
‹‹ወደብን አብሮ ማልማትና ማስተዳደር ለእኛ አዲስ ነው›› የሚሉት አቶ ካህሳይ፣ሌሎች ሀገሮች ለ50 ወይም ከዛ በላይ ዓመታት ስምምነት በማድረግ እንደሚያለሙና እንደሚያስተዳድሩ ይገልጻሉ፡፡ በርካታ ሀገሮችም ቋሚ ስምምነቶችን በማድረግ ወደብ በኪራይ እንደሚጠቀሙ የሚናገሩት አቶ ካህሳይ፣ ለዚህም ኬንያና ኡጋንዳን በአብነት ይጠቅሳሉ፤አገሮቹ በጋራ የማልማት ስምምነት ስላላቸው አብረው በመስራት ላይ እንደሚገኙም ነው የሚናገሩት።
ወደቡን ለማልማት የዋለው ወጪ ታስቦም ክፍያው ይቀንሳል፤ ‹‹ምን እያስገባህ እያስወጣህ ነው?›› የሚል ጥያቄም አይነሳም፤ ለማስገባት ወይም ለማስወጣት አሁን እንደሚደረገው ፍቃድ ሳይጠበቅ አብሮ የማስተዳደር የማልማት መብት የሚሰጥ አሰራር ነው ሲሉ ያብራራሉ።
ወደብ አልምቶ በጋራ መጠቀምን የሚከተሉት ወደብ የሌላቸው አገሮች ብቻ እንዳልሆኑም ጠቅሰው፤ ወደብ ያላቸው አሜሪካ ፣እንግሊዝ እና ካናዳም የጦር እና የንግድ መርከቦቻቸው የፈለጉትን ጭነት ይዘው ሲንቀሳቀሱ የራሳቸው ወደብ እንዲኖራቸው ስለሚፈልጉ እንደ ሚጠቀሙበት በመግለጽም አስፈላጊነቱን ያስገ ነዝባሉ።
ተመራማሪው ዶክተር በለጠ አንድ ስጋት አላቸው፤‹‹በጋራ ባለቤትነት ማልማትና ማስተዳደር የሚለው ሃሳብ በጣም አስቸጋሪ ነው›› ይላሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያታቸው አገራቱ ሉዓላዊ ናቸው፤ ከእነዚህ አገራት ጋር የሚገባው ስምምነት ችግሮችንም ሊያስከትል እንደሚችል ይጠቅሳሉ፡፡
አቶ ካህሳይ፣ በዶክተር በለጠ ሃሳብ አይስማሙም፡፡ በሁለት ሉዓላዊ አገራት መካከል የሚደረግ ስምምነትና ውል በዓለም አቀፍ ህጎች ተቀባይነት እንዳለው በመጥቀስም የሚያስከትለው ችግር እንደሌለ ያብራራሉ።
ስምምነቱ ምን ምንን ያካትታል የሚለው በሁለቱ አገራት የሚወሰን ሲሆን፣ ወደቡ ላይ የራሳቸው የሰው ኃይልና ቢሮ ይኖራቸዋል፤ በተለይ ኢትዮጵያ ሠራተኞቿ ግቡ ውጡ ሳይባሉና እቃውም በመጣበት ፍጥነት ቅድሚያ እየተሰጠው የመራገፍ ዕድል እንደሚያገኙ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹እነዚህ ነገሮች በውል ውስጥ በዝርዝር ከመካተታቸውም በላይ የእያንዳንዱ አገር መብትና ግዴታም ይጨመርበታል›› በማለት ያብራራሉ።
ረዳት ፕሮፌሰሩም የጅቡቲን ወደብ ብቻ በመጠቀም የአገሪቱን የወደብ ፍላጎት መሟላት እንደማይቻል ጠቅሰው፣ የሌሎች ሀገሮችን ወደብ አብሮ እያለሙና እያስተዳደሩ መጠቀሙ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ይናገራሉ።
‹‹አፍሪካ በርካታ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ያሉባት ብትሆንም፤ በፖለቲካል ሳይንስ ቋሚ ወዳጅም ሆነ ጠላት ስለሌለና ሁኔታዎችም በየጊዜው ስለሚቀያየሩ እነሱን ታሳቢ እያደረጉ መጠቀም ያስፈልጋል›› ይላሉ። ሥራው የጋራ ጥቅምን የሚያስከብር መሆኑን በመጥቀስም የአገራቱ ሉአላዊነት የሚያመጣው ችግር እንደማይኖርና ተባብሮ መስራትን ማሰብ እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ፡፡
እንደ አቶ ካህሳይ ገለጻ፤ እንደዚህ ዓይነት አሰራር በተለይም ለአልሚው አገር ከፍተኛ ጠቀሜታ ይሰጣል፡፡ ከዚህ አንጻርም ኢትዮጵያም ወደቡን በጋራ በማልማቷና በማስተዳደሯ በኢኮኖሚ፣ በፀጥታ፣ በማህበራዊና አካባቢያዊ ግንኙነቶች ላይ በጣም ተጠቃሚ ከመሆኗ ባሻገር ትስስሯንም ማጠናከር ያስችላታል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ባደገች ቁጥር የጎረቤት አገሮችም እያደጉ ይሄዳሉ›› የሚሉት አቶ ካህሳይ፣ ዕድገቱ ተወዳዳሪ ጥቅም የሚያስገኝ በመሆኑ ተያይዞ ለማደግ ችግሮችን ከስር ከስር እየተነጋገሩ መፍታትና በሥራውም ከከፍተኛ መሪዎቹ እስከ ታችኛው አካል የሚመለከተው ሁሉ ተሳትፎ እንዲያደርግበት ማስቻልም እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ።
በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሰነድ ላይ እንደተመለከተው፤በእቅድ ዘመኑ መጨረሻ አማራጭ ወደቦችን በመጠቀም የበርበራ ትራንዚት ኮሪደር ድርሻን ከምንም ወደ 30 በመቶ ማድረስ እንዲሁም የፖርት ሱዳን ትራንዚት ኮሪደር ድርሻን ከ2 በመቶ ወደ 10 በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል፡፡
‹‹ተጨማሪ ወደብ መፈለግ የሚለው ሃሳብ አሁን የመጣ አይደለም›› የሚሉት ዶክተር በለጠ፣ ከኤርትራ ነጻነት በኋላ የሁለቱ አገራት መልካም ግንኙነት ሲበላሽ በአንድ ወደብ ላይ መተማመን እንደማይቻል እና ተጨማሪ ወደቦችን ማፈላለግ እንደሚያስፈልግ ታምኖበት እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ያስታውሳሉ፡፡ይህን ተከትሎም ደቡብ ሱዳንን ጨምሮ ከኬንያ ጋር ላሙ ወደብን የማልማትና ኮሪደሩን የመጠቀም አካሄድ ተጀምሮ እንደነበር ይጠቅሳሉ። ሱዳንን፣ የበርበራን፣ የቦሳሶን ወደብ ለመጠቀም የተጀማመሩ ሥራዎች እንደነበሩም አመልክተው፤ይህ እውን ባለመሆኑ የተነሳም ሙሉ በሙሉ ወደ ጅቡቲ ወደብ መኬዱን ይጠቁማሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደቦችን በጋራ በማልማት ለማስተዳደር የሚያስችል ተግባር እያከናወኑ ይገኛሉ። በዚህም የጅቡቲንና የፖርት ሱዳን ወደብን ከፊል ክፍል በጋራ በማልማት ለማስተዳደር የሚያስችል ስምምነት መፈረሙን መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዚህ ቀደም ሲልም የበርበራ ወደብን 19 በመቶ ድርሻ በመያዝ በጋራ አልምቶ ለመጠቀም እየተሰራ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በቅርቡ ወደቦችን በጋራ በማልማት ለማስተዳደር የተደረጉ ስምምነቶች ተግባራዊ ከሆኑ ኢትዮጵያ እጅግ ተጠቃሚ ትሆናለች። ወደ አገሪቱ በሚገቡ እቃዎች ላይ የሚታየው የዋጋ ንረትም ይቀንሳል፤ የኢትዮጵያ ነጋዴዎችም ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ለመላክ ጅቡቲ ላይ የሚያወጡትን ከፍተኛ ወጪ በመቀነስ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮችን በመሳብ በኩልም ከፍተኛ ጥቅም ያስገኛል፡፡

ዜና ትንታኔ
እፀገነት አክሊሉ

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።