Items filtered by date: Wednesday, 09 May 2018

እአአ በህዳር 2018 መጀመሪያ በጋና አዘጋጅነት ለሚካሄደው 13ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የብሔራዊ ቡድኖች ማጣሪያ በወጣለት መርሀ ግብር እየተከናወነ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ በውድድሩ የሚሳተፉትን አገራት ለመለየት የመጨረሻው ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች በተያዘው ግንቦት ወር የመጨረሻ ሳምንት ይካሄዳሉ፡፡ ውድድሮቹ በተለያዩ አገራት ከተሞች ይካሄዳሉ። የአልጄሪያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድንን እና የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን (ሉሲዎችን) የሚያገናኘው ጨዋታ ግንቦት 26 ቀን 2010 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡
በአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ በተሳትፎ ታሪኩ ጠንካራ ቡድን ይዞ በመቅረብ የሚነገርለት የአልጄሪያ ብሄራዊ ቡድን ከሉሲዎቹ ጋር ላለበት ፍልሚያ ቅድመ ዝግጅቱን እያደረገ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ በአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ታሪክ ሶስት ጊዜ በመሳተፍ ታሪክ የሚታወቁት ሉሲዎችም ለጨዋታው ዝግጅታቸውን ከጀመሩ ሰንበት ብለዋል። የሊቢያ ብሄራዊ ቡድንን በመርታት ከመጨረሻው ምዕራፍ የደረሱት ሉሲዎቹ ሴኔጋልን በመጣል ከመጡት አልጄሪያዎች ጋር ይፋጠጣሉ።
የሁለቱ ቡድኖች ፍጥጫ ከሁለት ዓመት በፊት የነበረውን ተመሳሳይ የታሪክ ምዕራፍ ያስታውሳል፡፡ እኤአ በ2016 የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ለማለፍ በሚደረገው ማጣሪያ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሰራው ስህተት የሴቶች ብሄራዊ ቡድን (ሉሲዎች) በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ተሳታፊ አልነበረም። የአልጄሪያ ብሄራዊ ቡድን ደግሞ የመጨረሻውን ዙር ማጣሪያ ከቶጎ ብሄራዊ ቡድን ለማድረግ ተዘጋጅቷል። የቶጎ ብሄራዊ ቡድን ግን ባልተጠበቀ ሁኔታ በገዛ ፍቃዱ ራሱን ከጨዋታው ማግለሉ ተሰማ።
የአፍሪካ እግር ኳስ ማህበር /ካፍ/ የቶጎ ውሳኔ አስደንጋጭ ቢሆንበትም በወቅቱ ከማጣሪያ ውጪ የተደረገው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በማጣሪያው የሚሳተፍበት ዕድል ማግኘት ቻለ። ለሉሲዎቹ በአጋጣሚ የመጣው የተሳትፎ ሲሳይ ከአልጄሪያ ብሄራዊ ቡድን ጋር አፋጠጣቸው። የመጀመሪያው የጨዋታ ፍጥጫም በአልጀርስ ተደረገ። በጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከፍተኛ ጉጉትና ፍላጎት አሳዩ፡፡ ባለሜዳዎቹ አልጄሪያዎችና ሉሲዎች የነበራቸው እንቅስቃሴ ተቀራራቢ መሆኑ ደግሞ ፉክክሩን አጓጊ አድርጎታል። የማሸነፍ ፍላጎት ከሁለቱም ወገን አይሎ ቢታይም የአልጄሪያ ብሄራዊ ቡድን በቀዳሚነት ግብ ማስቆጠር ቻለ፡፡ ሉሲዎች የግብ እድል ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት ቢያርጉም በተቆጠረችባቸው አንድ ግብ ተሸንፈው ለመውጣ ተገደዱ፡፤
በአልጀርስ በጠባብ ውጤት ሽንፈትን ያስተናገዱት ሉሲዎች፤ በመልሱ ጨዋታ ውጤቱን ቀልብሰው ታሪክ ይሰራሉ የሚል ትልቅ ተስፋ ተጣለ። የአልጄሪያ ብሄራዊ ቡድን በበኩሉ በሜዳው በጠባብ ግብ የተቀዳጀውን ድል አስጠብቆ ለመውጣት እጅ ላለመስጠት ተዘጋጅቷል፡፡ በተለያዩ መላምቶች የታጀበው ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተካሄደ። በሁለቱም ቡድኖች የማሸነፍ ጉጉት የተነሳ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ሜዳ ላይ ቢታይም ጨዋታው በ1 ለ 1 አቻ ውጤት ተጠናቀቀ። ሉሲዎች ከሜዳቸው ውጪ ያጡትን ድል በሜዳቸው ለመመለስ ያደረጉት ጥረት አልተሳካም፡፡ በዚህም አልጄሪያዎች በ 2 ለ 1 ድምር ውጤት ወደ ካሜሮን ለመጓዝ የሚያስችላቸውን ትኬት መቁረጣቸውን አረጋገጡ፡፡
በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ላይ ይሄን መልክ ያዘለ ታሪክ ባለቤት የሆኑት የአልጄሪያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን እና የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ዳግም ተፋጠዋል። ሁለቱ ቡድኖች የመጨረሻው ዙር ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን አልጄሪያ ላይ ለማድረግ ቀጠሮ ይዘዋል። የአምናው ባለ ድል የሆኑት አልጄሪያዎች ታሪክን ለመድገም ተገቢውን ዝግጅት ማድረጉን ተያይዘውታል፡፡ ሉሲዎቹ በበኩላቸው ከሁለት ዓመት በፊት የነበረውን ቁጭት ለመወጣት ለጨዋታው ትልቅ ትኩረት ሰጥተዋል፡፡
በአሰልጣኝ ሰላም ዘርአይ የሚመራው የሉሲዎቹ ቡድን በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል። በአፍሪካ ዋንጫ የመሳተፍ ዓላማን የሰነቀችው አሰልጣኝ ሰላም፤ ከአልጄሪያ ጋር የሚደረገው ጨዋታ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ለአዲስ ዘመን ተናግራለች።
ግንቦት 26 አልጄሪያን የሚገጥሙት ሉሲዎች ከሰሞኑ በሩዋንዳ በሚካሄደው የመካከለኛውና ምስራቅ አፍሪካ የሴቶች ዋንጫ ላይ ይሳተፋሉ። በ2009 ዓ.ም በኡጋንዳ አዘጋጅነት በተካሄደው የሴካፋ ውድድር ላይ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ጠንካራ አቋም ያሳዩት ሉሲዎች፤ በዘንድሮው ውድድር የተሻለ ውጤት ያስመዘግባሉ የሚል ግምት አሳድራል። ተስፋ የተጣለባቸው ሉሲዎች ኪጋሊ በመግባት ልምምድ እያደረጉ ነው፡፡ ከኪጋሊው ውድድር መልስ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ አልጄሪያን ለመግጠም ወደ አልጀርስ የሚጓዙ ይሆናል።
ይህ የጨዋታ መደራረብ በቡድኑ ላይ ጫና ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት ያደረባቸው አካላት አሉ፡፡ እነዚህ አካላት የሴካፋው ውድድር በቡድኑ ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳርፍ በደንብ ሊታሰብበት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡ አሰልጣኝ ሰላም ግን « በሴካፋ መሳተፍ ከአልጄሪያ ጋር ለሚኖረው የማጣሪያ ጨዋታ አቅም ለመፍጠር መልካም አጋጣሚ ይሆናል »ትላለች።
ብሄራዊ ቡድኑ ምንም አይነት የወዳጅነት ጨዋታ አለማድረጉን የምትገልጸው አሰልጣኟ የሴካፋ ውድድር የቡድኑን አቋም ለመለካት ይረዳል ብላለች፡፡ በሴካፋ ውድድር ኬንያና ታንዛኒያን የመሳሰሉት ቡድኖች ይሳተፋሉ። የአልጄሪያ ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ኬንያን ከማጣሪያው ውጪ በማድረግ ነው ለዚህ የደረሰው፡፡ ስለሆነም አቅምን ለመለካት ውድድሩ ጠቃሚ መሆኑን አሰልጣኝ ሰላም ተናግራለች፡፡
«በሩዋንዳ አዘጋጅነት የሚካሄደው የሴካፋ ዋንጫ ውድድር ተሳትፎ ዋንጫ ወይም ውጤት ይዞ መምጣት አይደለም፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ላይ ጠንካራ ቡድን ለማዋቀር ጭምር ነው »ያለችው አሰልጣኟ፤ ወደ ስፍራው ለመጓዝ ለ24 ተጫዋቾች ጥሪ መደረጉን አስታውቃለች፡፡ ውድድሩ ታዲያ ከእነዚህ ተጫዋቾች የተሻለውን ምርጥ 11 እና ምርጥ 18 ተጫዋቾችን ለመለየት ያግዛል።
በቡድኑ ውስጥ ከመከላከያ ማርታ በቀለ፣ ከሐዋሳ ከተማ ዓባይነሽ ኤርቂሎና ምርቃት ፈለቀ፣ ከደደቢት መስከረም ኮንካ፣ ሰናይት ቦጋለ፣ ሎዛ አበራና ትዕግሥት ዘውዱ፤ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ትዕግሥት መዓዛ፣ ፅዮን እስጢፋኖስ፣ ታሪኳ ዴብኮ፣ ዙሌይካ ጁሃር፣ ሕይወት ዳንጊሶና ረሒማ ዘርጋው፣ ከቅዱስ ጊዮርጊስ መሰሉ አበራ፣ ብዙአየሁ ታደሰ፣ ቤዛዊት ተስፋዬና ቤተልሔም ሰማን፤ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ቤተልሔም ከፍያለውና ዓለምነሽ ደመቀ፣ ከዲላ ከተማ ገነማ ወርቁ፣ ከኢትዮጵያ ወጣቶች አካዳሚ አረጋሽ ካልሳ፣ ከጥረት ኮርፖሬሽን ታሪኳ በርገና፣ ከአዳማ ከተማ ሴናፍ ዋቁማና ከድሬዳዋ ከተማ ፀጋነሽ ተሾመ ወደ ስፍራው የተጓዙ ተጫዋቾች ሆነዋል።
«በሴካፋ ተሳትፏችን አቋማችንን በመለካት ወደ አልጀርስ እንጓዛለን፡፡ ከአልጄሪያ ጋር በሚኖረን ጨዋታ አሸንፈን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን። የመጀመሪያው ጨዋታችን ደግሞ አልጀርስ ላይ መሆኑ ለቡድኑ ስነልቦና ጥሩ ይመስለኛል። የተሠራውን ሥራ ለመገምገም ያግዛል፡፡ የመጀመሪያውን ጨዋታ በአሸናፊነት ለማጠናቀቅ የሚያስችል ዝግጅት አድርገናል። የተሰጠን ኃላፊነት ብሄራዊ ቡድኑን ለጋናው አፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ለማብቃት ነው›› ብላለች።
የአልጄሪያ ብሄራዊ ቡድን ከሉሲዎቹ ጋር የሚኖረውን የመጨረሻውን ምዕራፍ በአሸናፊነት ለማጠናቀቅ እጅ የሚሰጥ እንዳልሆነ ይነገራል፡፡ የአልጄሪያ ብሄራዊ ቡድን በማጣሪያ ጨዋታው ኬንያና ሴኔጋልን የመሳሰሉ በአፍሪካ ጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኙ ቡድኖችን በመጣል የመጣ በመሆኑ ሉሲዎችን እንደሚፈትን ተገምቷል፡፡ በዚህም የተነሳ የሉሲዎች የመጨረሻው የተሳትፎ ምዕራፍ ከባድ ይሆናል የሚል ግምት ተይዟል።
ከዚህም በተጨማሪ አልጄሪያ በፊፋ ወርሃዊ የደረጃ ሰንጠረዥ ከአፍሪካ ሰባተኛ፣ ከዓለም ደግሞ 62ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ቡድኑ 12 የሚደርሱ ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች አሉት። እነዚህ ተደማምረው ቡድኑ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለመራመድ የሚያደርገው ጉዞ ሊሳካለት እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡
ከዓለም 112ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት እና በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ መልካም የሚባል ታሪክ ያላቸው ሉሲዎችም ቢሆኑ ታዲያ ለአልጄሪያ ብሄራዊ ቡድን በቀላሉ እጅ እንደማይሰጡ ይጠበቃል። ሉሲዎች በአፍሪካ ዋንጫ ለሶስት ጊዜ ተሳትፈዋል፡፡ ከእነዚህ የተሳትፎ ታሪኮች እኤአ በ2004 አራተኛ ደረጃ በማግኘት ከፍተኛ የሚባለውን ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ የዓለም ዋንጫን የመሰለ ትልቅ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ከሚያስችላቸው አጋጣሚ እስከ መቃረብ የደረሰ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት በአልጄሪያ ብሄራዊ ቡድን ተሸንፈው ከተሳትፎ ውጪ መሆናቸው ቁጭት ያሳደረባቸው ሉሲዎች በአልጄሪያው አቻቸው ላይ ድልን ለመቀዳጀት ተዘጋጅተዋል፡፡ ታሪክ ራሱን በመድገም ሉሲዎችና የአልጄሪያ ብሄራዊ ቡድንን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዳግም አፋጧል፡፡ ቡድኖቹ ወደ ዋንጫው ውድድር ለማለፍ የመጨረሻዎቹ 180 ደቂቃዎች ብቻ ቀርተዋቸዋል፡፡
የማጣሪያውን የመጀመሪያ ጨዋታ በአልጄሪያ የሚያደርጉት ሉሲዎች ከአምስት ቀናት በኋላ በሜዳቸው በአዲስ አበባ ስታዲየም የመልስ ጨዋታ እንደሚያደርጉ የወጣው መርሀ ግብር ያስረዳል፡፡ በእነዚህ ሁለት ከተሞች የሚደረገው ጨዋታ፤ ከሁለት ዓመት በፊት ለአልጄሪያ ብሄራዊ ቡድን ፈንጠዚያ፤ ለሉሲዎች ቁጭትና ንዴት ሆኖ ያለፈውን ታሪክ ይደግመው ይሆን? ወይስ ተቃራኒ ውጤት ተመዝግቦ ሉሲዎችን ለድል ያበቃል? የሚለው የብዙዎች ጥያቄና ጉጉት ነው፡፡ የአልጀርስና የአዲስ አበባው ጨዋታዎች ምላሹን ይሰጣሉ፡፡ ድል ለሉሲዎቹ !

 

  ስፖርታዊ ጨዋነትን ለማስፈን ሚኒስቴሩ ቸልተኝነት አሳይቷል ተባለ

 

በስፖርታዊ ጨዋነት እና ስነ-ምግባር ዙሪያ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር አዘጋጅነት ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በትናንትናው ዕለት በአዳማ ከተማ በይፋ ተጀምሯል።

በመድረኩም በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የህክምና ዳይሬክተር ዶክተር አያሌው ጥላሁን በአገሪቱ ስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ችግሮችና መንስኤዎቻቸውን የተመለከተ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቧል።
ዶክተር አያሌው እንደገለጹት፤ በአገሪቱ በስፋት እየተስተዋለ ለሚገኘው የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል የስፖርቱ ባለድርሻ አካል የሆነው የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አንዱ ነው። በተለያዩ ስታዲየሞች የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለቶች ቢከሰቱም፤ ሚኒስቴሩ ችግሮችን እያየ ዝምታን መምረጡ እንደ ጉድለት እንደሚታይ በጥናቱ ተመልክቷል። ሚኒስቴሩ ከፌዴሬሽኑ ጋር ተቀራርቦ አለመስራቱ የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት ሚዛኑን እንዲስት ሌላው ምክንያት ነው፡፡ ፌዴሬሽኖችን የሚቆጣጠርበት መንገድ ደካማ መሆኑ፣ በጥናትና ምርምር የታገዘ ድጋፍና ክትትል እያደረገ አይደለም፡፡
በእግር ኳስ ፌዴሬሽን በኩል የሚታየው ጉድለት ሌላው መንስኤ መሆኑ በጥናቱ የተጠቀሰ ሲሆን፤ አለም አቀፍ ህጎችና ደንቦች ሳይሸራረፍ ተግባራዊ አለማድረጉ እንደ ችግር ተነስቷል። በፌዴሬሽኑ የተዋቀሩ የዳኞች፣ የውድድር፣ የፀጥታ፣ የዲሲፒሊን እና የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴዎች አደረጃጀት እና አሰራር ባህላዊ መሆን፣ ጥፋት በሚፈፅሙ ክለቦች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ጠንካራና ሌሎችን የሚያስተምር አለመሆን እና የውሳኔዎች ወጥ አለመሆን በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በኩል የታዩ ድክመቶች ናቸው፡፡

በስፖርታዊ ጨዋነት ዙርያ የሚያተኩረው የምክክር መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው


በክለቦች በኩል የሚታዩ ክፍተቶች ሌላው የችግሩ መንስኤ መሆናቸውን ዶክተር አያሌው አስረድተዋል፡፡ ለዚህም የክለቦች አደረጃጀት እና አሰራር በሰዎች ፍላጎት እንጂ አለም አቀፍ መመርያና ደንብን ተከትሎ አለመሆን ፣ የክለብ አመራሮች ስለ እግር ኳስ ያላቸው ግንዛቤ ውስን መሆን ፣ የክለብ አመራር አካላት በማንኛውም ሁኔታ ውጤቱን ማግኘት እንጂ፤ ለስፖርቱ፣ ለተመልካቹ፣ ለተጫዋቾችና ለሚዲያው የማይጨነቁ መሆናቸውን አንስተዋል። የችግሩ ባለድርሻዎች አሰልጣኞች መሆናቸው የጠቆመው ጥናቱ፤ ከወቅታዊ የእግር ኳስ ህጎች ጋር ራስን አለማዘጋጀት፣ የዳኝነት ውሳኔንና የጨዋታ ውጤትን በፀጋ አለመቀበል፣ ተጨዋቾችን መቆጣጠር አለመቻል፣ ራሳቸው የችግሩ አካል መሆናቸው፣ ውጤት ሲጠፋ ውጫያዊ ሰበቦችን መፍጠር የችግሩ መንስዔ መሆናቸው በጥናቱ ተመላክቷል።
በአገሪቱ በስፋት ለታየው የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር ተጫዋቾች ባለድርሻ መሆናቸውን ጥናቱ አንስቷል። ለዚህም የእግር ኳስ ህግ ግንዛቤ አለመዳበር፣ ለስፖርቱ እና ለራሳቸው ክብር ዋጋ አለመስጠት፣ ስሜታዊነት፣ ተመልካቾች እና ደጋፊዎችን ለፀብ ማነሳሳት፣ ያልተገባ አጨዋወት በመጠቀም ጉዳት በማድረስ የጨዋታውን መንፈስ ማደፍረስ ከመንስኤዎቹ መካከል ናቸው ተብሏል።
በጥናቱ ዳኞችም ባለድርሻ መሆናቸው የተጠቀሰ ሲሆን፤ ዳኞች የአካል ብቃት ማነስና የስነ ልቦና ዝግጅት አለማድረግ፣ ከውድድር በፊት ከክለብ አመራሮች ጋር አላስፈላጊ ግንኙነቶች ማድረግ፣ የፍትሀዊነት ችግር፣ በዳኞች መካከል ተናቦ ጨዋታዎችን የመምራት ችግር በማሳያነት ቀርቧል፡፡ አንዳንድ የሚዲያ አካላት የሚያቀርቡት ዜና ሚዛናዊ አለመሆን፣ በሜዳ ላይ የተሰራውን ስህተት እና ፌዴሬሽኑ የሚሰጠውን ውሳኔ መቃወምም ለችግሩ የራሳቸው ድርሻ አላቸው ነው የተባለው፡፡
የፀጥታ አካላት ክለቦችን በክልላዊ ስሜት መደገፍ መጀመር ለችግሩ መንስዔ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡ ሁኔታዎችን በቸልተኝነት መመልከት፣ ስለስፖርት ደህንነት ጥልቅ ግንዛቤ አለመኖር በማሳያነት መቅረቡን ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርና ከሶከር ኢትዮጵያ የተገኙት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

 

ዳንኤል ዘነበ

 

 

 

 

Published in ስፖርት
Wednesday, 09 May 2018 17:48

ጉደኞቹ ጋዜጠኞች

ሚያዚያ 03 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ መዝናኛ አምድ ላይ የቀረበውን የ‹‹ጉደኛዋ ጋዜጠኛ›› ታሪክን አነበብኩት። ይህ ጽሁፍ የአንዳንድ ጋዜጠኞችን ያልተገባ ስነ- ምግባር አስታወሰኝ፡፡ እናም በዚህ ፅሁፍ ተንተርሼ “ጉደኞቹ ጋዜጠኞች” በሚል ርዕስ በጋዜጠኝነት ህይወቴ ካየኋቸው አጋጣሚዎች ጥቂቱን ለማጋራት ወሰንኩ፡፡ ለዛሬ ከታዘብኳቸው ከብዙዎቹ  ጥቂቱን እነሆ!

ሁሌም እንደ ፋሲካና የዘመን መለወጫ ያሉ በዓላት በደረሱ ጊዜ አንዳንድ ሀይማኖታዊ ተቋማት የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞትና መልዕክት ለማስተላለፍ ሚዲያዎችን መጥራታቸው የተለመደ ነው። ከጋዜጣዊ መግለጫው እና ቡራኬ በኋላም በስፍራው ለተገኙ ጋዜጠኞች እና የካሜራ ባለሙያ ዎች ለዶሮ መግዣ እንዲሁም ለበረከት ሲሉ መቶም፣ ሁለት መቶም ብር መሰጠታቸውን መቼም ሁሉም ያውቃል፡፡
በእንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ታዲያ ጋዜጠኛ ያልሆነ ሁሉ ከጋዜጠኛ ጋር ጋዜጠኛ መስሎ ይቀርባል። ብዙ ጊዜም ጉዳዩ የማይመለከታቸው አንዳንድ የስፖርት ጋዜጠኞች ሳይቀሩ ለብሪቷ ሲሉ ብቻ ብቅ ማለታቸው አይቀሬ ነው፡፡ እንዲሀ ሲሆንም መግለጫው የሚሰጥበት አዳራሽ ሞልቶ መቀመጫ ጠፍቶ ይጨናነቃል፡፡
ታዲያ አንድ ቀን ከእነዚህ ሀይማኖታዊ ተቋማት መካከል አንዱ ወሳኝ የሚባል ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ለሚዲያዎች ጥሪ አቀረበ። መግለጫው የአውደ አመት መልካም ምኞት የሚተላለፍበት አልነበረምና በስፍራው የተገኘነው ሦስት ጋዜጠኞች ብቻ ነበርን፡፡ ይህ እውነታ አንዳንድ ጋዜጠኞች ሙያዊ ሥነ-ምግባሩን ከጠበቀ ዘገባ ይልቅ የገንዘብ እና ቁሳቁስ ጥቅም ወደሚያስገኝ ሥራ ማዘንበላቸውን ያመላክታል፡፡
አንድ ጊዜ የያኔው የሞሪሸየስ አምባሳደር ቦሌ አካባቢ በሚገኝ አንድ ሆቴል መግለጫ ይሠጡ ነበር፡፡ በወቅቱ ‹‹አበል (ቡጬ) ይሰጣል›› በመባሉም ብዙ ጋዜጠኞች እና ጋዜጠኛ ያልሆኑት ሁሉ ተገኝተው ነበር፡፡ ብዙ ግዜ እንዲህ አይነት ቦታ ከመገኘቱ ብዛት “አይታጤ” ያልነው አንድ ጋዜጠኛ መሰልም ከመሀላችን ሆኖ የመግለጫውን መጀመር ይጠባበቃል፡፡
ይህ ሰው በየትኛውም የመገናኛ ብዙኃን ተቋም ሰርቶ አያውቅም። ሁሌም በእንዲህ አይነት ቦታ ሲገኝና “ከየት ነህ?” ሲባል ግን ካልተገኙት ሚዲያዎች መሀል አንዱን ጠርቶ ከዚያ ነኝ ማለት ልማዱ ነው፡፡ ዛሬ ‹‹ከአዲስ ዘመን›› ካለ ነገ ‹‹ከአዲስ አድማስ›› ለጥቆ ‹‹ከሬዲዮ ፋና... ›› ይላል፡፡ አንድ ቀን ታዲያ ከሬዲዮ ፋና የተላከ ጋዜጠኛ መኖሩን ሳያውቅ ‹‹ከሬዲዮ ፋና›› በማለት ስሙን ያስመዘግባል፡፡ ሳያስበው ታዲያ ለእሱ መጥፎ የሚባል ክስተት ተፈጠረ። በወቅቱ የተፈጠረው ክስተት ራሱን የቻለ ሃተታ ስለሚሆን ወደ ሞሪሸየሱ አምባሳደር መግለጫ ልመለስ፡፡
በመግለጫው ከሞላ ጎደል ሁሉም መገናኛ ብዙኃን ስለነበሩ ‹‹አይታጤም›› ተገኝቷል።እኔም ከየት እንደሚል ለማወቅ ጓጉቻለሁ። እናም ፈጠን አልኩና ከኋላው ተሰለፍኩ፡፡ አጅሬ ታዲያ መቼ የዋዛ ሆነ፡፡ ከየት ነህ? ሲባል “ከኒውስ ፔፐር” አለላችኋ! እሱ እኮ! ጥቅማ ጥቅም (ቡጬ) የሌለበት አካባቢ ዝር አይልም፡፡
ከአሥር ዓመታት በላይ በዘለቀው ጋዜጠኝነቴ ብዙ ጉደኛ ጋዜጠኞች አጋጥመውኛል፡፡ አንዳንድ ጋዜጠኞች ከሙያዊ ሥነ-ምግባር ይልቅ የግል ጥቅም አሳዳጅ ወይም በተለምዶ አጠራር ‹‹ቡጬ›› ሰብሳቢ ሲሆኑ አይቻለሁ፡፡ ይህ በሥነ-ምግባር ታንጸው ለሙያው ልዕልና የሚሰሩትን ባለሙያዎች አይጨምርም፡፡ጥሩ ሥነ-ምግባር በማስፈን እና ባለማስፈን ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማቱም ቢሆኑ የራሳቸው ሚና እንዳላቸው ይታወቃል፡፡
አንዳንዶቹ በመልካም ሥነ-ምግባር እንደሚመሩ እኔው ራሴ የአይን ምስክር መሆን እችላለሁ፡፡ እስከማውቀው ድረስ እንዲህ አይነቶቹ ጋዜጠኞች በአንዳንድ ጥቅም ተደልለው የተለየ ዘገባ አይሠሩም፡፡ ‹‹ዜና ልስራልህ? ስንት ትከፍለኛለህ? በአየር ሰዓቱ ስለአንተ ጥሩነት ላውራና ምን ትሰጠኛለህ?›› በማለትም አይደራደሩም፡፡ እንዲህ አይነቶቹ መልካም ሥነ-ምግባር የተላበሱ ጋዜጠኞች ለሌሎች አርአያ የሚሆኑ ናቸው፡፡
የአዲስ ዘመኗ ጸሀፊ ስለ አንዲት ጋዜጠኛ አለባበስ እና አጠያየቋን አስመልክታ የተደመመችበ ትን አንስታለች፡፡ ስለ አጠያየቅ ከተነሳ እኔም ስለምን ጉዳይ፣ ማንን እንደሚጠይቁ ያልገባቸው ጋዜጠኞች ስለመኖራቸው ጥቂት ልበል፡፡ አቃቂ ቃሊቲ የሚገኘው ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ሲመረቅ የተገኘ አንድ ጋዜጠኛ ለጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ የሰነዘረውን “ጥያቄ” መቼም አልረሳውም፡፡
ምን ዓይነት ጥያቄ ይጠይቅ ይሆን? ተብሎ ሲጠበቅ አጅሬው ‹‹የሆስፒታሉ መገንባት ለአካባቢው ማኅበረሰብ ምን ይጠቅማል ብለው ያስባሉ?›› ብሎ እርፍ፡፡ የሆስፒታልን ጠቀሜታ እንኳ በዘርፉ ረጅም ጊዜ ያሳለፉና ዕውቀት ያላቸው ከፍተኛ አመራር፤ ሌላው ሰውም አይጠፋውም፡፡ ታዲያ አንዳንዶቹ እንዲህ አይነቱን አይተው ‹‹ጋዜጠኛ ለመሆን ምንም ዕውቀት አያስፈልግም›› ቢሉ ይፈረድባቸዋል?
ወደ አለበባስ ስመለስ በራሴ የደረሰውን አልረሳም፡፡ በግሌ ከልብሱ አይነት ይልቅ ለንጽሕናው ትኩረት እሰጣለሁ፡፡ በአንድ ወቅት ታዲያ የጀርመኗ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ኢትዮጵያን በጎበኙ ጊዜ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በተጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ሙሉ ልብስ ሳልለብስ በሸሚዝ ብቻ ተገኘሁ።ይህ በመሆኑም ከአንድ የስራ ባልደረባዬ የደረሰብኝ ግሣፄ እና ምክር አሁንም ድረስ አብሮኝ አለ፡፡
በ“ጉደኛዋ ጋዜጠኛ” ጽሁፍ ላይ እንደተጠ ቀሰው ሚዛን የማያነሳ ጥያቄ ከመጠየቅ ባሻገር መረጃውን በአግባቡ ያለማስተላለፍ ችግርም ይስተዋላል፡፡ የህዝብ አፍ እና ጆሮ የሆኑበትን ሙያ ለግል መጠቀሚያ ማዋላቸው ያሳዝናል፡፡ በዚህ የግል ጥቅምን ለማሟላት በሚደረግ ሩጫ ከቤት ቁሳቁስ እስከ ዘመናዊ ሞባይልና ሌሎችን ቁሳቁሶችን መሟላታቸውን የሚናገረውን ሲናገሩ መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡
አንድ ቀን ወፍራም አበል ይከፈልበታል በተባለ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከአንድ የጋዜጣ ተቋም አራት ጋዜጠኞች ተገኙ፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫው እስኪጀመር እንኳን ተራ ወሬ አጭር ልቦለድ ተጽፎ ያልቃል፡፡እናም ጨዋታው እንደተለመደው ቀጥሏል። ከእነሱ መሀል የቱ ዜና የትኛው ትንታኔ እንደሚጽፍ አይታወቅም። በዕለቱ የነበሩ ሌሎች ጋዜጠኞች ‹‹ ከሮናልዶ እና ከሜሲ ቀጥሎ ከፍተኛ ገቢ ያላቸው እነዚህ አራት ጋዜጠኞች ናቸው›› ሲሉ እንደተሳለቁባቸው አስታውሳለሁ ጊዜው ትንሽ ቢርቅም፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ብዙ የምለው ቢኖረኝም ለዛሬው በዚህ ይብቃኝ፡፡ በመዝናኛው ዓምድ የተፃፈው ርዕሰ ጉዳይ ብዙ አወያይቶናል፤ አስታውሶናልና ፀሐፊዋንና አዲስ ዘመን ጋዜጣን ሳላመሰግን አላልፍም፡፡ በሥነ-ምግባር የታነጹ ጋዜጠኞችን ማፍራት ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ሳይሆን ሁላችንንም የሚመለከት ነው፡፡

መልካሙ ተክሌ

Published in መዝናኛ
Wednesday, 09 May 2018 17:47

በስጋት የሚራመዱ እግሮች

በርካቶች  በትራፊክ አደጋ  ሳቢያ ከወጡበት  አልተመለሱም። ውጥናቸውን ሳይቋጩ በጅምር ለመተው ተገደዋል፡፡ ብዙዎችን ያለቤተሰብ፣ ጧሪና ደጋፊ፣ የሚያስቀረው የትራፊክ አደጋ የማይድን ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት አድርሷል ፤ ሀብትን አውድሟል፤ኢኮኖሚን አቃውሷል፡፡ አደጋው በአካል ጉዳተኞች ላይ ሲያጋጥም የአስከፊነቱ መጠን በእጅጉ  ይጎላል። የአዲስዘመኗ መልካምስራ አፈወርቅም የትራፊክ አደጋና የአካል ጉዳተኞችን ስጋት በተመለከተ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ያገኘችውን ተሞክሮ እንዲህ ታጋራናለች።

 

በየቀኑ ማለዳ የሚጠበቅባትን ግዴታ አትዘነጋም። ገና ከቤቷ ስትወጣ የሚቆያትን ሀላፊነት ጠንቅቃ ታውቃለች። እሷ ትውልድን የማብቃትና ዕውቀትን የመዝራት ዓላማዋ የጸና ነው። ለአመታት በቆየችበት የመምህርነት ሙያ በርካቶችን ለቁም ነገር አብቅታለች፡፡ በነጭ በትሯ እየተመራች ጉዞዋን ስትቀጥል መንገዷ ሁሌም በስጋት እንደተሞላ ነው፡፡ ጠዋት ያለፈችው ሜዳ ስትመለስ ገደል፣ በሰላም የተራመደችው ጎዳናም ወደ ኋላ ጉድጓድ የሆነበት ጊዜ ብዙ ነው።
መምህርት ፈትለወርቅ አሰፋ ይህ ሁሉ ውጣ ውረድ የህይወቷ አንድ አካል እንደሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል። ዘወትር በየመንገዱ የሚገጥማት ፈተናም ከባድ ነው። ያም ሆኖ ግን ይህን እውነታ በውጣ ውረድ ልታልፈው ግድ ይላታል።
መምህርት ፈትለ በየጊዜው የእሷን መድረስ በጉጉት ለሚናፍቁ ተማሪዎቿ በእጅጉ ታስባለች፣ ትጨነቃለች። በሰአቱ ገብታ የሚፈልግባትን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣትም ትወጥናለች። እሷ ዕውቀትን ለተራቡ ወገኖች ያላትን ሁሉ ስታበረክት አዕምሮዋ በደስታ ይረካል። እንዲህ ሲሆን የየዕለቱን ፈተናዎቿን ሁሉ ትረሳለች ። ስለነገው ውሎዋም በአዲስ መንፈስ ታስባለች።
አንድ ቀን መምህርት ፈትለወርቅ ከቤቷ ርቃ ከመንገድ ዳር ቆማለች። የምትጠብቀው አውቶቡስ ደረሰና ትኬት ቆርጣ ወደ ውስጥ ገባች። ከጥቂት ጉዞ በኋላ በየፌርማታው መቆም የጀመረው አውቶቡስ የሚገቡትን እያሳፈረ፣ የሚወርዱትንም እያቃለለ ጉዞውን ቀጠለ። ፈትለወርቅ ሁሌም የምትሄድበትን ቦታ ታውቃለች። ከምትፈልገው ስትደርስም በአግባቡ ወርዳ ወደ ትምህርት ቤቷ ታመራለች።
የዛን ዕለት የተሳፈረችበት አውቶቡስ በእጅጉ ፈጣን እንደነበር አትዘነጋም። እሷ ከምትፈልገው ቦታ እንደደረሰች «ወራጅ፣ ወራጅ» በማለት ምልክት ሰጠች። ሾፌሩ በወጉ አልሰማትምና የፍጥነት ጉዞው አልተገታም። ቆይቶ ግን ደጋግማ መናገሯን ባወቁ ተሳፋሪዎች ጉትጎታ አውቶቡሱ ቆሞ በሩ ተከፈተ። ፈትለ ሁሌም ከምትወርድበት ቦታ መራቋን አውቃለች። ከደረሰችበት ስፍራ ከመውረድ ሌላ ምርጫ አልነበራትም።
በጉጉት የሚጠብቋትን ተማሪዎች እያሰበች በተከፈተው በር ፈጥና ወረደች። አወቶቡሱም በሩን ደርግሞ ወደፊት ተፈተለከ። አይነስውሯ ፈትለ ነጭ በትሯን ዘርግታ ለመራመድ እግሮችዋን አነሳች። እንዳሰበችው ሆኖ ግን ቀና መንገድ አልገጠማትም። ከቆመችበት ራመድ እንዳለች ክፍት የነበረ ጥልቅ ጉድጓድ ተቀበላት። ወዲያውም መላው አካሏ ተጎድቶ ለከፋ ስቃይ ተዳረገች። ሁኔታውን ያዩ እግረኞች ለእርዳታ ፈጥነው ደረሱላት። በአካባቢው የነበረ የትራፊክ ፖሊስም አውቶቡሱን ተከታትሎ በቁጥጥር ስር አዋለው ።
ፈትለወርቅ በሾፌሩ እገዛ ከሆስፒታል ደጃፍ ደረሰች። ጥቂት ቆይቶ ግን ግለሰቡ እዛው ትቷት ከአካባቢው መሰወሩን ተረዳች ።ለሶስት ወራት አልጋ ይዛ የታከመችባቸው የህመም ጊዜያት ለአይነስውሯ መምህርት ክፉ ትዝታ እንደሆኑ ቆይተዋል። እሷን ጨምሮ ሌሎች ጓደኞችዋ በየጊዜው በእንዲህ አይነቱ የአደጋ ስጋት ውስጥ መሆናቸው አሁንም ድረስ ያሳስባታል።
አቶ ካሳሁን ሀብተ ጊዮርጊስም ዘወትር የሚያልፍባቸው ያልተመቹት መንገዶች ሁሌም በስጋት እንዲራመድ አድርገውታል ።እሱን ጨምሮ በርካታ አይነስውራን ራቅ ካሉ ስፍራዎች ወደ መሀል ከተማ የሚያደርጉት ጉዞ ምንግዜም ከአደጋ የራቁ አለመሆናቸውን ይናገራል። አቶ ካሳሁን ብዙ ግዜ አይነስውር ያልሆኑ ወገኖችን እርዳታ ይጠይቃል። ይህን በማድረጉም መጠቀሙን ነው የሚናገረው።
ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ሲኖርና ያልተመቹ መንገዶች ሲያጋጥሙ የሌሎችን እርዳታ መጠየቅ ተገቢ መሆኑን የሚያምነው አቶ ካሳሁን አንዳንድ አይነስውራን እግረኞች ይህን ለማድረግ ባለመፍቀዳቸው ለከፋ ጉዳትና ሞት እንደሚዳረጉ ይገልፃል፡፡ ይህ አጋጣሚ ደግሞ የብዙዎችን ልብ የሚሰብርና በተመሳሳይ ህይወት ውስጥ ለሚኖሩ አይነስውራንም የዘወትር ስጋትና ጭንቀት ነው።
አቶ ካሳሁን ከሁለት ዓመት በፊት በስድስት ኪሎ አካባቢ የተከሰተውን መጥፎ አጋጣሚ አይረሳም። በዚህ ስፍራ የሚኖሩ ሁለት ሴት አይነስውራን ተማሪዎች በመንገዱ ዳርቻ ሲሄዱ በደረሰባቸው የመኪና አደጋ የአንዷ ህይወት ወዲያውኑ አለፈ።ሌላዋም ለከፋ ጉዳት ተዳረገች። እነዚህን መሰል አጋጣሚዎች ሁሌም በአይነስውራን ላይ የሚያንዣብቡ የአደጋ ስጋቶች ናቸው።
አቶ ተካልኝ ዱጌም በየዕለት እንቅስቃሴው የአይነስውራን መንገድ ምቹ አለመሆኑ በስጋት እንዲራመድ አስገድዶታል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ለአይነስውራን እየተባሉ የተዘጋጁ መንገዶች መኖራቸውን ያደንቃል።የእነዚህ መንገዶች መዘጋጀት ብቻ ግን የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ መፍትሄ እንደማይሆን ይናገራል።
እንደ እሱ አባባል ከከተማዋ የለውጥ ሂደት ጋር ተያይዞ ለአይነስውራን በተዘጋጁ መንገዶች ዙሪያ በቂ የግንዛቤ ሥራ አልተሰራም። መንገዶቹ ከዋናው መተላለፊያ በቢጫ ቀለም መለየታቸውን ከሌሎች ጠይቆ መረዳቱን ይገልጻል። ልክ እንደ እሱ ሁሉ ብዙ አይነስውራን ስለመንገዱ ጠቀሜታና ዓይነት ምንም የተሰጣቸው ምክርና ገለፃ የለም። አስቀድሞም ቢሆን ከጉዳዩ ባለቤቶች ጋር ውይይት አለመደረጉን ይጠቁማል፡፡ በቢጫ የተለየው የዓይነ ስውራን መንገድ ከነጩ በትር ጋር ያለው ስምምነት ሳይጠና ነው ተግባራዊ የተደረገው ይላል፡፡ በመሆኑም መንገዶቹ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ አይደለም፡፡
እንደ አቶ ተካልኝ ዕምነት የእነዚህ መንገዶች ከነጭ በትር ጋር በአግባቡ አለመናበብ አይነስውራን ከእግረኞች መስመር ወጥተው ከመኪና ጋር እንዲጋፉ አስገድዷቸዋል። በየጊዜው የሚቆፈሩ ጉድጓዶችና ለውበት ሲባል በእግረኛ መንገዶች ላይ የሚተከሉ ዛፎችም ዓይነ ስውራን አቅጣጫቸውን ስተው የመኪና አደጋ ሰለባ እንዲሆኑ እያደረጉ ነው። የኤሌክትሪክ ኃይል ምሰሶዎችና የእግረኞች መንገድ ለመኪኖች መቆሚያነት መዋል ለአብዛኞቹ አካል ጉዳተኞች ችግር ሆነዋል፡፡
በከተማዋ የእግረኛ ማቋረጫዎች አካባቢ ምን ያህል መሳሪያዎች ለአይነ ስውራን የድምጽ መረጃ ይሰጣሉ? የሚለውም ያልተመለሰ ጥያቄ ነው። ይህ መሆኑም ብዙዎች በሰው እርዳታ ላይ ብቻ እንዲመረኮዙ እያደረገ ይገኛል።በአንዳንድ ቦታዎች ያሉትና በድምጽ የሚታገዙትም ቢሆኑ የሚሰጡት የቀለም አይነት ጥቆማና ፍጥነት ለተግባር የሚያመች አለመሆኑን አቶ ተካልኝ ይናገራል።
በእግረኞች መንገድ ላይ በየጊዜው የሚቀመጡ የግንባታ ቁሳቁሶች የአካል ጉዳተኞች ሌላው ፈተና ነው፡፡ አሁንም እየተባበሰ የመጣው የጎዳና ላይ ንግድ የበርካታ አካል ጉዳተኞችን እንቅስቃሴ እየተፈታተነ ይገኛል፡፡ በተለይም አይነስውራን በዚህ ግርግር መሀል ነጭ በትራቸው ቢሰበር አንድ እርምጃ መራመድ አለመቻላቸው የጉዳዩን አሳሳቢነት ያሳያል፡፡
ጥሩወርቅ ጥላሁን በነጭ በትሯ እየተመራች መንገድ ከማቋረጥ ውጭ የሌሎችን እርዳታ አትጠይቅም። በጉዞዋ አጋጣሚ ታዲያ የመንገዶቹ አመቺነት የተለያየ ሆኖ አግኝታዋለች። አንዳንድ ቦታዎች ለጉዞ የተሻሉ ናቸው ቢባሉም አብዛኞቹ ወጣገባ የበዛባቸውና ለመራመድ የሚያዳግቱ በመሆኑ እርምጃዋን ሁሉ ፈታኝ ያደርጉታል። ለዚህም እንደምሳሌ የምታነሳው ከሀያሁለት እስከ መገናኛ ድረስ ያለውን መንገድ ነው ።
እሷ እንደምትለው ይህ መንገድ ፈጽሞ አይነስውራንን ያላማከለ ነው።በጉዞዋ አጋጣሚ እንዳረጋገጠችውም መንገዱ ለነጭ በትር ማንሸራተቻ የሚያመች አይደለም። በቢጫ የተሰመረው መንገድ እንደ ጅማሬው ለሁለት እግሮች ማሳረፊያ መሆኑ ቀርቶ በቀጭኑ እየቀጠነ የሚሄድበት ሁኔታ ይስተዋላል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአጭር ርቀት የሚጓዘው መስመርም በየመሀሉ ቁፋሮዎች ያቋርጡታል። ወደ መንገዱ ገባ ብለው የሚሰሩ የንግድ ቤቶች ደረጃዎችም ተጨማሪ መሰናክሎች ይሆናሉ። ይህን መሰሉ ዕንቅፋት ሲያጋጥም ከእግረኞች መንገድ በመውጣት በመኪኖች መተላለፊያ ላይ መጓዝ ግድ ይላል።ይህም ለአስከፊ የመኪና አደጋና ለሌሎች ጉዳቶች ይዳርጋል።
ወይዘሪት መሰረት ለገሰ ሁሌም ከአካባቢዋ ስትርቅ የከተማ አውቶቡሶችን ትጠቀማለች ።በእግሮቿ ላይ ያለው ጉዳት ግን መንገዷን በምቾት እንድትቀጥል አያስችላትም። ለዚህ እንደምክንያት የምትጠቅሰው የመንገዶችን ምቹ ያለመሆን ነው። የድጋፍ መሳሪያዎችን አለመያዝዋ ሰዎች የጉዳቷን መጠን እንዳይረዱ አድርጓል። በመሆኑም ከሌሎች በተለየ ትኩረት አላገኘችም።
ይህም ብቻ አይደለም፣ መሰረት አውቶቡስ ስትጠቀም ብዙ ጊዜ በትክክለኛው ቦታ(ፌርማታ) አይቆሙላትም። ተሳፋሪዎችም አስቀድመው መንገድ ስለማይለቁ ለመውረድ ስትል ወድቃ የተጎዳችባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። እሷን ጨምሮ ሌሎች አካል ጉዳተኞችም በዚህ መሰሉ አጋጣሚ ለመኪና አደጋ ተጋላጭ የሚሆኑባቸውን አጋጣሚዎች መኖራቸውን ትጠቁማለች፡፡
የክራንች ተጠቃሚዋ ነጻነት ቀንአ ዘወትር በመንገድ ላይ የሚያጋጥሟት ፈተናዎች ብዙ ናቸው።በየጊዜው ከቤቷ ወጥታ መንገድ ስትጀምር እርምጃዋ ሁሉ በስጋት የተሞላ ነው። በተለይ ትራንስፖርት ለመያዝ በሚኖረው ግፊያና ትርምስ እንደ እሷ አይነት የአካል ጉዳት ያለባቸው ወገኖች ለትራፊክ አደጋ የመጋለጣቸው ችግር ሁሌም ያሳስባታል።
በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ በየጊዜው በከተማዋ የሚከሰተውን የትራፊክ አደጋ መነሻ በማድረግ ከተለያዩ የአካል ጉዳተኞች ማህበር ተጠሪዎችና ተወካዮቻቸው ጋር ውይይት አካሂዷል።በዕለቱም ሁሉም ተሳታፊዎች የችግሩን አሳሳቢነት ከአካል ጉዳተኝነት ጋር በማዛመድ የበኩላቸውን ሀሳብ ሰንዝረዋል፡፡
በጅማ ዩኒቨርስቲ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ጌታቸው ጥላሁን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በመንገድ ትራፊክ አደጋ ሳቢያ በዓመት አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ እንደሚሞት ይናገራሉ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሚያጋጥመው የአካል ጉዳትም ከ20 እስከ 50 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የችግሩ ሰለባዎች ናቸው። በተለይም ከ18 እስከ 29 አመት ዕድሜ ያላቸው ወጣቶች በአደጋው ህይወታቸውን ማጣታቸው የችግሩን አሳሳቢነት ያጎላዋል። ከእነዚህ መሀል የአካል ጉዳተኞች ቁጥር ቀላል ባለመሆኑ በመንገድ ደህንነት ላይ የሚኖረው ግንዛቤ ሊዳብር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በየቀኑ የተለያዩ የመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋን እንሰማለን። አይኖቻችንም ይህን እውነታ ይመለከታሉ።ሁላችንም ብንሆን በምንራመድበት መንገድ በአፍታ ቆይታ ስለሚገጥሙን አደጋዎች ልናውቅ አይቻለንም። በተለይም አካል ጉዳተኛ ወገኖች ራሳቸውን በማያድኑበት ሁኔታ ችግሩን ማስተናገዳቸው የአስከፊነቱን ደረጃ ከፍ ያደርገዋል፡፡ ከምንም በላይ ግን ለአደጋ መፈጠር ምቹ ናቸው የሚባሉ ሁኔታዎችን በማስወገድ አሳሳቢውን ችግር መታደግ የሁላችንም ሀላፊነት ሊሆን ይገባል።

 

Published in ማህበራዊ

ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በኢትዮጵያ እየተስፋፋ መምጣቱ ይነገራል፡፡ በህገ ወጥ መንገድ ስልክ በማስደወል የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል በመፈፀም አገሪቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እንድታጣ እየተደረገ ነው፡፡ የባንክን ሥራ ተክቶ በመስራት አገሪቱ ታገኝ የነበረው የውጭ ምንዛሬ እንዲቀንስ የማድረግ ወንጀሎችም በብዛት እየተፈፀሙ ነው፡፡ በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የተደራጁ፣ ድንበር ተሻጋሪና አገራዊ ጉዳት የሚያስከትሉ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ከሆኑት አቶ ብርሀኑ ወንድማገኝ ጋር በነበረን ቆይታ የሰጡንን መረጃ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

የተደራጁ፣ ድንበር ተሻጋሪና አገራዊ ጉዳት የሚያስከትሉ ወንጀሎች


የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 በአዲስ መልክ ከተደራጀ በኋላ አጠቃላይ የወንጀል አይነቶችን በአራት ትላልቅ ዘርፎች አደራጅቶ እየመራ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ ዘርፎች መካካል አንዱ የተደራጁ፣ድንበር ተሻጋሪና አገራዊ ጉዳት የሚያስከትሉ ወንጀሎች ዳይሬክቶ ሬት ነው፡፡ በዚህ ስር በሽብርተኝነትና ከሽብርተ ኝነት ጋር ተያያዥ የሆኑ ወንጀሎች ይካተታሉ፡፡
ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ የሚባሉት በህገ መንግስቱና በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ናቸው፡፡ የፀረ ሽብር አዋጅን በመተላለፍ የሚፈጸሙ ወንጀሎች፤ እንዲሁም፣ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍና ተመሳሳይ ወንጀሎችም በዚህ ስር ይካተታሉ፡፡

የተደራጀና ድንበር ተሻጋሪ የሚባሉት ደግሞ ዓለም አቀፍ ህግን ጭምር ጥሰው የሚፈጸሙ ወንጀሎች ናቸው፡፡ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ንግድ፣ በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ፣ በዲፕሎማቶችና በባለስልጣ ናት ላይ የግድያ ሙከራ ማድረግና ግድያ መፈጸምን ዳይሬክቶሬቱ የሚመለከታቸው ወንጀሎች ናቸው፡፡
የህዝብ ሁከት የሚያስከትሉ ተግባራት፤ አውሮፕላኖችና መርከቦችን የደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ወንጀሎች አገራዊ ጉዳት የሚያስከትሉ ወንጀሎች በሚለው ሥር ይካተታሉ፡፡ በሁለት ክልሎች መካካል የሚከሰቱ የብሄር ግጭት ወንጀሎችን የማየት ኃላፊነት አለበት፡፡ የባንክን ስራ ተክቶ መስራት ሌላው በዳይሬክቶሬቱ ክትትል የሚደረግበት ወንጀል ነው፡፡ እነዚህ በተለይ ውጭ አገር ሆነው አገር ውስጥ ባሏቸው ወኪሎች አማካኝነት ህገ ወጥ የሃዋላ አገልግሎት የሚሰጡትን ይመለከታል፡፡ በህገ ወጥ መንገድ ስልክ በማስደወል የቴሌኮም ማጭበርበር የሚፈፀም ወንጀልም አለ፡፡ በዚህም ኢትዮ ቴሌኮም በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር እንዲያጣ እየተደረገ ነው፡፡


በብዛት የሚፈፀሙ ወንጀሎች


መጠናቸው ቢለያይም ከላይ የተጠቀሱት ሁሉም ወንጀሎች በአገሪቱ ይፈፀማሉ፡፡ የቴሌኮም ማጭበርበርና የባንክን ስራ ተክቶ የሃዋላ አገልግሎት የመስጠት ወንጀሎች ከፍተኛ ድርሻ አላቸው፡፡ በህገ ወጥ መንገድ ስልክ የማስደወል ወንጀል በብዛት ተፈፅሟል፡፡ በዚህ ህገ ወጥ ድርጊት የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችም ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
መንግስት በይቅርታ ክሳቸውን ካቋረጠላቸው በተጨማሪ በሽብርተኝነት የተከሰሱ ብዛት ያላቸው መዝገቦች አሉ፡፡ በዚህ ወንጀልም በርካታ መዝገቦች ውሳኔ አግኝተዋል፡፡ በተያዘው ዓመት ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ወንጀል ጨምሯል፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት አምስትና ስድስት የነበረው መዝገብ ዘንድሮ በሚገርም ሁኔታ ወደ 15 አሻቅቧል፡፡ ለዚህም ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን የሚከላከል ራሱን የቻለ ህግ አለመኖሩ ለወንጀሉ መስፋፋት በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡
ይህ ወንጀል ከአጠቃላይ የአገር ሰላምና ደህንነት ጋር በተያያዘ በተደነገገ ህግ ብቻ እንዲታይ መደረጉ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል አዳጋች ሆኗል፡፡ እናም የሚመለከተው ህግ አውጭ አካል ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት መስጠት ይኖርበታል፡፡


በሽብርተኝነት የተከሰሱ ተጠርጣሪዎች


አቃቤ ህግ ክስ ለመመስረት የሚከተላቸው አካሄዶች አሉ፡፡ በመጀመሪያ ፖሊስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምርመራ ያካሄዳል፡፡ አቃቤ ህግ የተሰበሰቡ የተለያዩ ማስረጃዎችን አይቶ ያስከስሳል ወይም አያስከስስም የሚለውን በማየት ይወስናል፡፡ ይህ ሂደት ታልፎ ወደ ክስ ይኬዳል፡፡ ክሱ በፍርድ ቤቱ ሚዛንና ዕይታ ሲታይ የማሸነፍና የመሸነፍ ሁኔታ ይኖራል፡፡
የአልሸባብን ቡድን አባላትን ጨምሮ በሽብርተኝነት የተከሰሱ አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ የተከሰሱ ሰዎች በአብዛኛው ክሳቸው እየተነሳ ነው፡፡ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በአራት ዙር ክሳቸው የተነሳላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ከፍትህ መዘግየት ጋር ተያይዞ ቅሬታ ሊቀርብ ቢችልም ዳይሬክቶሬቱ ማስረጃውን አይቶና መርምሮ ክስ ያቀርባል፡፡ በቀጣይ ክፍተቶችን ለማስተካከል ጥረት ይደረጋል፡፡


አገራዊ ጉዳት የሚያስከትሉ ወንጀሎች


በብሄር ግጭት ጉዳይ ክስ የተመሰረተባቸው መዝገቦች አሉ፡፡ በቀጠሮ ላይ ካሉት መዝገቦች በተጨማሪ በርካታ መዝገቦች ላይ ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ለምሳሌ በደቡብ ክልል መዠንግር ወረዳ በቀጠሮ ላይ ያሉ ተከሳሾች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ከየመን ሲመጣ በአውሮፕላኑ ውስጥ ረብሻ በመፍጠር ስድስት ዓመት የተፈረደበት አንድ የመናዊ ዜጋ ክስ ተመስርቶበታል፡፡
የባንክ ስራ ተክቶ በመስራት ወንጀልም የተከሰሱ አሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው አሜሪካ ሆኖ በኢትዮጵያ ባሉት ወኪሎች አማካኝነት ገንዘብ ለሚላክለት ሰው በዶላር ሳይሆን በብር እንዲሰጡት በማድረግ ዶላሩን እዚያው ያስቀረዋል ፡፡ ዶላሩ በባንክ ቢላክ ኖሮ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ታገኝ ነበር፡፡ ይህን በአገር ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት የሚያስከትለውን ወንጀል ለመከላከል ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት በትብብር መስራት አለባቸው፡፡ በቴሌኮም ማጭበርበር በአገር ላይ የሚደርሰውን ከፍተኛ ጉዳት ለመታደግ የሁሉም የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ ነው፡፡


የማስቀጣት አቅም


ብዙ ወንጀሎች በክልሎች፣ በየምድብና በየቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ይታያሉ፡፡ የማስቀጣት አቅሙም እንደ ክልሎቹና ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ይለያያሉ፡፡ በማዕከል ደረጃ ብቻ ያለውን ስንመለከት ባለፉት ዘጠኝ ወራት 95 መዝገቦች ቀርበው በ93 ቱ ላይ አቃቤ ህግ ክስ እንዲመሰረት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ በተመሳሳይ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በክስ ሂደት ላይ ከነበሩ 151 መዝገቦች በ131 ላይ በፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ አሰጥቷል፡፡ ከእነዚህም 18 ከባድ ፣ 94 በመካከለኛ እና 19 ቀላል የወንጀል መዝገቦች ናቸው፡፡ በ20 መዝገቦች የነጻ ውሳኔ የተላለፈ ሲሆን ከእነዚህም ዐቃቤ ህግ በሰባቱ ላይ ይግባኝ ጠይቋል፡፡
በከባድ ወንጀሎች ላይ የማስቀጣት አቅም መቶ በመቶ ደርሷል፡፡ በመካከለኛ 82 በመቶ፣በቀላል 95 በመቶ ደርሷል፡፡ ምስክር ባለመቅረብ የተነሳ አልፎ አልፎ መዝገቦች የሚቋረጡበት ሁኔታ አለ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከሳሽና ተከሳሽ በመስማማትም ተከሳሽ ያለመቅረብ ሁኔታ ይከሰታል፡፡ የተወሰኑ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ በሰጣቸው የዋስ መብት ተጠቅመው በዋስ ሲለቀቁ ከአገር የሚወጡ ተከሳሾች ያጋጥማሉ፡፡ እነዚህ የማስቀጣት አቅሙ እንዲቀንስ ያደርጋሉ፡፡


በፍትህ ስርዓቱ የዜጎችን ሮሮ ለማስቀረት


ነጻ ገለልተኛና ሚዛናዊ ፍትህን መስጠት ከሁሉም ይጠበቃል፡፡ ጉዳዮች ሳይንዛዙና ቀጠሮዎች ሳይበዙ አቃቤ ህግ አፋጣኝ ውሳኔ መስጠት ይኖርበታል፡፡ ከላይ እስከ ታች ባለው የፍትህ አካላት መዋቅር የዜጎችን ፍላጎት ለማርካት ሁሉም ተቋማት ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ የህግ ባለሙያው አቅሙን እያዳበረ እውቀቱን እየገነባ በመሄድ ለህብረተሰቡ የተፋጠነ አገልግሎትና ውሳኔ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ ቀጠሮ ሲበዛና ሲደጋገም ህዝቡ ስለሚንገላታ ቅሬታ ያነሳል፡፡ በወቅቱ ፈጣን ውሳኔ መስጠት ‹‹የዘገየ ፍትህ እንደ ቀረ ይቆጠራል›› የሚለውን አባባል ስለሚያስቀር በዚህ ላይ በደንብ መስራት ይገባል፡፡
ለፍርድ ቤት የሚቀርቡ ሁሉም የክስ መዝገቦች የተለያዩ አካላትን ትብብርና ቅንጅት ይጠይቃሉ፡፡ ከምርመራ እስከ ውሳኔ ማሰጠት ያለው ሂደት የአቃቤ ህግ፣ የፖሊስና የፍርድ ቤትን ትብብር ይሻሉ፡፡ ይህ የትብብርና ተናቦ የመስራት ሂደት በቀጣይም ሊጠናከር ይገባል፡፡ በማስረጃ ምዘና፣ ከምርመር እስከ ማስወሰን ያለውን ሂደት ለማቀላጠፍ የሚረዱ አቅጣጫዎች በአግባቡ መተግበር አለባቸው፡፡ ህግን የማስከበር ኃላፊነት በጥንቃቄና በትኩረት ሊሰራ ይገባል፡፡


ከአወቃቀር፣ ከአሰራርና ከሰው ኃይል ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ክፍተቶችና ጉድለቶችን ማስተካከል ይገባል፡፡ ጠቅላይ ዓቃቤህግ ከህዝቡ ጋር የግንኙነት መድረክ እየፈጠረ ነው። አወቃቀርና አሠራሩን ለማስተካከል ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው። በክልሎች ዘጠኝ ፣ በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ክፍለ ከተሞች ቅርንጫፍ ከፍቷል። አገልግሎቱን ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ ጅማሮው ጥሩ ቢሆንም ከዚህ የበለጠ ግን መስራት ግድ ይላል፡፡ ፍርድ ቤቶች፣ፖሊስና ማረሚያ ቤቶች በትብብር መስራት ከጀመሩ ስምንት ዓመት አልፎቸዋል፡፡ ይህንን ይበልጥ በማጠናከር የህዝቡን እርካታ ለማረጋገጥ መረባረብ ያስፈልጋል፡፡

ጌትነት ምህረቴ

Published in ፖለቲካ

መንግሥት በ2002 ምርጫ ማግስት የመጀ መሪያውን የዕድገትና ትራንስፎር ሜሽን ዕቅድ ይፋ አደረገ። በድህነት ላይ ላነጣጠረው ዕቅድ ህዝብ መንግሥትን "አበጀህ" በማለት ድጋፉን ሰጠ። መንግሥትን አበጀህ ካስባሉት ዕቅዶች መካከል ደግሞ አስሩ አዳዲስ ስኳር ፋብሪካዎች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡
መንግሥት በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ 2 ነጥብ 25 ሚሊዮን ቶን ስኳር ለማምረት ግብ አስቀምጧል፡፡ ከዚህም ውስጥ አንድ ነጥብ 246 ሚሊዮን ቶን ስኳር ለዓለም ገበያ በማቅረብ 661 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር የማግኘት ዓላማን ሰንቋል፡፡ ለ200ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር የሥራ አጡን ቁጥር የመቀነስ ግብ ነበረው፡፡
መንግሥት በአምስት ዓመት ለማሳካት ቃል የገባው፤ ህዝቡም ተስፋ ያደረጋቸው ስኳር ፋብሪካዎች ታዲያ ከሰባት ዓመት ተኩል በኋላም እንደታሰበው ሆነው አልተገኙም፡፡ አንድም ፋብሪካ በተሟላ ደረጃ ወደ ሥራ ገብቶ ማምረት አለመቻሉ ተስፋው ሁሉ የህልም እንጀራ ሆነ።
የጉዞው መጀመሪያ
መንግሥት ለመገንባት ያቀዳቸው ስኳር ፋብሪካዎች በደቡብ ክልል ኦሞ ኩራዝ አምስት ፣ በአማራ ክልል ሦስት፣ አንድ በትግራይ ክልል ወልቃይት እና ቀደም ብሎ በአፋር ክልል የተጀመረው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካዎች ናቸው፡፡ የፋብሪካዎቹ ግንባታ ዕቅድ ይፋ መሆኑን ተከትሎ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተከናወኑ፡፡ ለፋብሪካዎቹ ግንባታ የሚሆን ገንዘብ ከቻይናና ከህንድ መንግሥታት በብድር፤ ቀሪው ከአገር ውስጥ በብድር እንዲመቻች ተደረገ፡፡
ነባርና አዳዲሶቹን ስኳር ፋብሪካዎች በባለቤት የሚያስተዳድርና የሚያስገነባው ስኳር ኮርፖሬሽን በአዋጅ ተቋቋመ ቁጥር የአራቱ ፋብሪካዎች ግንባታ በአገሪቱ ግዙፍ ኢንዱስትሪ ሆኖ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በ2002 ዓ.ም ለተቋቋመው ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ብኢኮ) ተሰጡ፡፡ ሌሎቹ ፋብሪካዎች በቻይናና ህንድ ኩባንያዎች ተይዘው ወደ ሥራ ተገባ፡፡
የአብዛኛዎቹ ስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ በ18 ወራት እንደሚጠናቀቁ ጊዜ ገደብ ተቀመጠላቸው፡፡ መንግሥትም ሁሉንም ፋብሪካዎች በመጀመሪያ የዕቅድ ዘመን እንደሚያጠናቅቅ ቃል ቢገባም እስከ አሁን የኦሞ ቁጥር ሁለት ስኳር ፋብሪካ የሙከራ ምርት መጀመሩ ከመነገር ያለፈ የታየ ተጨባጭ ምርት የለም፡፡ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሦስት እየተጠናቀቀ መሆኑ በተደጋጋሚ ቢገለጽም ሥራ አልጀመረም። የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ 94 ነጥብ4 በመቶ ደርሷል ከተባለ ወራት ቢቆጠርም አሁን ላይ ውል የማቋረጥ ሂደት ላይ መሆኑ ነው የተነገረው። ተጠናቀቀ የተባለው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካም በገጠመው ብልሽት ማምረት ማቆሙ ነው የሚነገረው።
በጣና በለስ ከሚገነቡት ቁጥር አንድ ፋብሪካ 78 ነጥብ 1 በመቶ ፤ ቁጥር ሁለት 25 በመቶ ደርሰው ብረታ ብረትና አንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ፕሮጀክቱን በማዘግየቱ ግንባታቸው ተቋርጧል። ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ቁጥር አንድ ውሉ በመቋረጥ ላይ ሲሆን ቁጥር ሁለት ውሉ ተቋርጦ ለሌላ ተቋራጭ ለመስጠት በሂደት ላይ ነው። እየተፋጠነ መሆኑ የሚነገርለት የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ግንባታ ከ67 በመቶ አልዘለለም፡፡ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አምስት ስኳር ፋብሪካ ግንባታም ገና በጅማሮ ላይ ነው፡፡ ስኳር ኮርፖሬሽን ለመገንባት ቃል ከገባቸው አስሩ ስኳር ፋብሪካዎች በ2009 ዓ.ም በአቅም ችግር ምክንያት ግንባታቸው የተቋረጡ መኖራቸው የሚታወስ ነው፡፡
መንግሥት በመጀመሪያ የዕድገትና ትራንስፎ ርሜሽን ዕቅድ እንደሚሳኩ ቃል ገብቶ ወደ ሥራ ያስገባቸው ፋብሪካዎች ባለመጠናቀቃቸው በህዝብ ዘንድ ቅሬታ እየፈጠሩ ነው። በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ ስኳር ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ግብ የያዘችው ኢትዮጵያ በየዓመቱ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ስኳር ለማስገባት ተገዳለች፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት እስከ አሁን ድረስ ብቻ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ገዝታለች፡፡ ተጨማሪ አንድ ሚሊዮን ኩንታል በመግዛት ሂደት ላይ ነች።
የፋብሪካዎቹ ግንባታ መዘግየት የዜጎችን ‹‹የእንችላለን›› መንፈስ መሸርሸራቸውም ነው የዘርፉ ምሁራን የሚናገሩት፡፡ ፋብሪካዎቹ በተያዘላቸው ጊዜ ዕውን ሆነው ለአገልግሎት አለመብቃታቸው ስኳርን በሚፈለገው ጊዜና መጠን ለማግኘት ትልቅ ተስፋ በሰነቀው ህዝብ ላይ ከፍተኛ ቅሬታን ፈጥረዋል፡፡ የአገር ውስጥ ስኳርን ለሚናፍቀው ዜጋ ስኳር በሽታ መሆናቸውም ነው የሚነገረው፡፡
የስኳር ኮርፖሬሽን የኮሚዩኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጋሻው፤ ዕቅዱ ወገብ የሚያጎብጥ በመሆኑ ከኩራዝና ከበለስ አንዳንድ ፋብሪካዎችንና እርሻዎችን መቀነሱን የኮርፖሬሽኑና የሥራ ተቋራጩ የማስፈጸም አቅም ውስንነት፣ የዲዛይን ለውጥ፣ የማሽነሪና የመለዋወጫ እጥረት፣ የፋይናንስ
የፋብሪካዎቹ የቅርብ አዳሪነት መንስዔ
በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህሩ ዶክተር ካሳሁን ዱባለ፤ መንግሥት ትልቅ ማቀዱ ተገቢ ቢሆንም ዕቅዱ በራሱ ግብ አይደለም ይላሉ። የታቀደው በተያዘለት ጊዜና ገንዘብ ካልተከናወነ በአገር ላይ ኪሳራ እንደሚያደርስ ይናገራሉ፡፡ የስኳር ፋብሪካዎቹ ግንባታ መዘግየት አገሪቱን እያከሰሯት፤ መንግሥትንም እምነት እያሳጡት መሆኑን ያብራራሉ።
ዕቅዶቹ ወደ መሬት ከመውረዳቸው በፊት በማን ይሠራሉ? እንዴት ይሠራሉ? የሚሉት ጥያቄዎች በዕውቀት፣ በጥናት፣ በአደረጃጀትና በአሠራር በተሟላ መልኩ መመለስ እንደነበረባቸው ዶክተር ካሳሁን ይናገራሉ፡፡ ይህ አለመሆኑ ፋብሪካዎቹ እንዲጓተቱና እንዲቋረጡ አድርጓል፡፡
እሳቸው እንደሚያብራሩት ፕሮጀክቶቹ የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶላቸው የፋይናንስና የሥራ አፈፃጸማቸው በጠንካራ ሥነ ምግባር አለመመራቱ፣ ሁሉም ባለድርሻዎች ተቆጥሮ የተሰጣቸውን ሥራ በተቀናጀና በኃላፊነት አለመወጣታቸው፣ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ተቆጣጣሪዎች አፈጻጸማቸውን በመገምገም ለእያንዳንዱ ችግር መፍትሄ እየሰጡ አለመሄዳቸው፤ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች በአገራዊ ስሜት ግዴታቸውን አለመወጣታቸው ለችግሩ በመንስዔነት ይጠቀሳሉ፡፡ ብዙ ልምድና አቅም ለሌለው ብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን አራት ፋብሪካዎችን እንዲገነባ መስጠቱም ሌላው ችግር ነው፡፡
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ኡጋ ዋቅፌሌ፤ ለስኳር ፋብሪካዎቹ መጓተት የተለያዩ ምክንያቶችን ይጠቅሳሉ፡፡ የፕሮጀክቱ በባለሙያዎች አለመመራት፤ አለመናበብ፤ ወደ ሥራ ከመገባቱ በፊት ሥራዎቹን በወረቀት ላይ በጊዜ ወስኖና ባለቤት ሰጥቶ አለመግባት፣ የባለሙያዎች የአቅም ችግር፣ የተመደቡት ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ሙሉ ጊዜያቸውን በሥራቸው ላይ አለማሳለፍን ያነሳሉ፡፡ በኦሞ ኩራዝ ፕሮጀክት ለሥራ በሄዱበት ወቅት የፕሮጀክቱ አሰሪዎቹ በቦታው አለመገኘታቸውንና ተናቦ የመስራት ችግር እንዳለ መታዘባቸውን በማሳያነት ያቀርባሉ፡፡
የኢኮኖሚክስና የፖለቲካ ምሁሩ አቶ ካህሳይ ገብረየሱስ፤ የፕሮጀክቱ ባለቤቶችና ሥራ ተቋራጮች፣ የሚመለከታቸው ሚኒስቴር ቤቶችና ሌሎች ተቋማት፤ እንዲሁም ተቆጣጣሪዎቹ የፕሮጀክቱን የዕቅድ አፈፃጸም በጋራ በመገምገም መፍትሔ አለመስጠታቸው ችግሩ እንዲፈጠር አድርጓል ይላሉ፡፡
አገሪቱ የገጠማት አገራዊ የፖለቲካ ችግር፣ አቅምን አውቆ ወደ ሥራ አለመግባት፣ በሂደት ለሚያጋጥሙ የአስተዳደር ችግሮች የመፍትሔ ሀሳብ በማቅረብ የሚፈታ የተደራጀ የምርምር ማዕከል አለመኖር ፋብሪካዎቹ ባሉበት እንዲሄዱ አድርጓል፡፡ በብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ብቻ ሳይሆን በቻይናና በህንድ የሚገነቡ ፋብሪካዎችም ተመሳሳይ የመዘግየት ችግር ማጋጠሙን ያክላሉ፡፡
ምክር ቤቱ ኃላፊነቱን ተወጥቷል
የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን አለመጠናቀቅ አለመቻሉን ያምናሉ። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ገብረ እግዚአብሄር አርዓያ፤ የመጀመሪያው የዕቅድ ዘመን የፋብሪካዎቹ ግንባታ የዝግጅት ምዕራፍ እንደነበር በመጠቆም በሁለተኛው የእቅድ ዘመን ወደ ሥራ መገባቱን በመግለፅ ችግሩን ለማስተባበል ይሞክራሉ።
የአንዳንድ ፋብሪካዎች ግንባታ መዘግየቱን ጠቁመው ምክር ቤቱ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ቁጥጥር ማድረጉን ይናገራሉ፡፡ ቁጥጥር አልተደረገም የሚለው ትችት ተገቢ አለመሆኑን በማንሳት በተጓተቱ ፋብሪካዎች ላይ በወቅቱ የቴክኖሎጂ፣ የኮንትራት አስተዳደር እና ሌሎች ግምገማዎች መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ግምገማውንም ለስኳር ኮርፖሬሽንና ለብረታ ብረት ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን፤ እንዲሁም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፈጉባዔው በኩል በ2009 ዓ.ም በመላክ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል፡፡
አቶ ገብረ እግዚአብሔር እንደሚሉት፤ የአገሪቱ አቅም በፈቀደ ፋብሪካዎቹ እየተገነቡ ናቸው፡፡ ለፋብሪካዎቹ የተመደበው ገንዘብ አልጠፋም፡፡ የወጣው ገንዘብና የሥራ አፈጻጸም ብዙም ልዩነት የለውም። ምክር ቤቱ በሰው ሀይል አስተዳደር፣ በኪራይ ሰብሳቢነት፣ በሙስና ዝርዝር ግምግማ በማድረግ በዋና ኦዲተርና በስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን በማረጋገጥ ችግር ካለ እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል፡፡
የፋብሪካዎቹ ግንባታ ዳግም እንዳይከሽፍ
መንግሥት የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ያላሳካውን የስኳር የተለያዩ የስኳር ፋብሪካዎቹን ግንባታ ለማስቀጠል ዩኒቨርሲቲዎችን በማሳተፍ በእውቀት ላይ የተመሰረተ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ዶክተር ኡጋ ያስገነዝባሉ፡፡ ጥብቅ ቁጥጥርና የተቀናጀ አሠራር መዘርጋት የፋብሪካዎ ቹን ግንባታ ከፍፃሜ ለማድረስ ያስችላል፡፡ ዶክተር ካሳሁን፤ በበኩላቸው የተቋረጡትም ሆነ በግንባታ ላይ ያሉት ፋብሪካዎች የዘገዩበትን ትክክለኛ ምክንያት በመገምገም፣ ችግሮቹን በመለየት፤ጠንካራ ማስተካከያ ማድረግ ይገባል ይላሉ፡፡
እንደ ዶክተር ካሳሁን አባባል፤ የችግሩ መንስዔ ተለይቶ በጥናት ላይ ሳይመሰረት ከአንዱ ቀምቶ ለቻይና ሥራ ተቋራጭ መስጠት ለችግሩ መፍትሄ አይሆንም። ፓርላማው ችግር ከመፈጠሩ በፊት በየጊዜው እየገመገመ ከወሬ ማድመቂያ ያለፈ ማስተካከያ ማድረግ አለበት። ውድቀትን መለካት ሳይሆን በእያንዳንዱ ሂደት ከውድቀቱ በፊት የማስተካከያ እርምጃ መውሰዱ ነው የሚመከረው፡፡ በዚህ መልኩ መስራት ከተቻለ ፋብሪካዎቹን ከዳግም ውድቀት መታደግ ይቻላል፡፡
‹‹የተደራጀና የተቀናጀ የማስፈጸም እርምጃ መውሰድ ይገባል›› የሚሉት አቶ ካህሳይ፤ ሥራ ተቋራጭ መቀያየር ‹‹ጉልቻ ቢቀያይሩት ወጥ አያጣፍጥም›› ከመሆን አይዘልም ይላሉ፡፡ ፓርላማው የችግሩን መንስዔ በደንብ ያውቃል የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልፀው ሪፖርት ከማድመጥ ባለፈ ይህን ለማወቅ የሚያስችል ተቋምና አቅም በመፍጠር ቁጥጥር ማድረግ እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡ የአሠራር ስርዓት ማበጀት፣ በቀጣይ ግንባታ የአገር ውስጥና የውጭ ሥራ ተቋራጮችን ልምድና አቅም በጥንቃቄ በመለየት ወደ ሥራ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡
ባለድርሻ አካላት አንዱ ከሳሽ ሌላው ተከሳሽ ከመሆን ሂደት ወጥተው ለውድቀቱም ሆነ ለስኬቱ ድርሻቸውን በመውሰድ ለመፍትሔ መረባረብ አለባቸው፡፡ ሁሉም ተጠያቂ መሆናቸውን በመገንዘብ የሚሰጣቸውን ኃላፊነት ቆጥረው በመረከብ መፈጸም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከውጭና ከአገር ውስጥ የሚገኙ የኢንዱስትሪዎ ችን የአፈጻጸም፣ የአስተዳደርና የምርምር ልምድና እውቀትን የሚያከማችና የሚያስተላልፍ የኢንዱስትሪዎች ስትራቴጂክ ማዕከል ማደራጀት ይገባል፡፡ ለፖሊሲ አውጭዎች የዕድገት አማራጭ መፍጠር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰበሳቢ አቶ ገብረ እግዚ አብሄር እንደሚሉት፤ የተጓተቱት ፕሮጀክቶች ውላቸው ፈርሶ በአዲስ እንዲገነቡ እየተደረገ ነው፡፡ ኦሞ ኩራዝ ሦስት በመጠናቀቅ ላይ ሲሆን፤ የወልቃይት ስኳር ፋብሪካም 67 በመቶ ደርሷል። ኦሞ ኩራዝ ሁለት ማምረት ጀምሯል፤ ኦሞ ኩራዝ አምስት ወደ ግንባታ ገበቷል። ሌሎቹ ፋብሪካዎችም ግንባታቸው ተጠናቆ የሁለተኛው እቅድ ስኬታማ እንደሚሆን ሙሉ እምነት አለው፡፡
ሁለተኛው ዕቅድ ከከሸፈ
የፋብሪካዎቹ ግንባታ በሁለተኛው እቅድ ዘመን ካልተሳካ ህዝብ በመንግሥት ላይ እምነት እንደሚያጣ ዶክተር ካሳሁን ይናገራሉ፡፡ የህዝቦችን ተነሳሽነት ያዳክማል፤ አገሪቱን ለዕዳ ይዳርጋል፤ ድህነትንም ያባብሳል፡፡ አላስፈላጊ ወጭን ስለሚያስከትልም በቀጣይ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ያስቸግራል፡፡ የአገሪቱን ቁጠባ ከማዳከሙም በላይ አገሪቱ በአበዳሪዎች እምነት እንድታጣ ያደርጋል።
አቶ ካህሳይ፤ በበኩላቸው ለፕሮጀክቶቹ የሚወጣው ገንዘብ በብድርም ቢገኝ በህዝቡ ነው የሚከፈለው፡፡ መንግሥት በህዝብ ሀብት የሚያስገነባው ፕሮጀክት ተፈፃሚ ሳይሆን ሲቀር ህዝብ የልማትና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄን ያነሳል፡፡
ችግሩን ለመፍታት በትኩረት መሥራት ይገባል፡፡ የህዝብን ሀብት በየበረሃው እያባከኑ መቀጠል እንደማይቻል መንግሥትም ሆነ ግለሰቦች መገንዘብ አለባቸው። ፋብሪካዎቹ በተጓተቱ ቁጥር ከስኳር ይልቅ የስኳር በሽታ ዓይነት ትልቅ መዘዝ ይዘው እንደሚመጡ በአግባቡ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ስለሆነም ችግሮችን በደንብ በመፈተሽ፣ በመገምገምና የመፍትሔ አቅጣጫ በማስቀመጥ ለግንባታዎቹ ዕውን መሆን መረባረብ ይገባል፡፡

አጎናፍር ገዛኸኝ

Published in ኢኮኖሚ

የዓለማችን ሃያሏ አሜሪካን ከፕሬዚዳንት ጆርጅ ዋሽንግተን እስከ ወቅቱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ 45 ያህል መሪዎችን አፈራርቃለች።ሃያሏን አገር በመሪነት ለማስተዳደር ታጭተውና ተመርጠው ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት መግባት ከቻሉት መሪዎች ሁሉ እንደ ወቅቱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአነጋጋሪነት ብቅ ያለ መሪ አለመኖሩን ብዙዎች ይናገራሉ። የአሜሪካ ቀንደኛ ተፎካካሪ ከሚባሉት ከሁለቱ ፓርቲዎች አንዱ ከሆነው ሪፐብሊካን ቤት የተገኙት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ገና ስልጣን ከመጨበጣቸው ነበር የሃሳብ ተቃርኖ ማንጸባረቅ የጀመሩት።
ሰውዬው፤ ይህ አይነቱን መንገዳቸውን በማስቀጠል ወደ ስልጣን እስከመጡበት ብሎም በመሪነት መጓዝ እስከ ቻሉበት ጊዜያት ድረስ ወትሮም በሚታወቁበት በግራ አጋቢ ንግግራቸው፣በሚያመነጩት ሃሳብ፣ በድርጊታቸውና በአቋማቸው ለአሜሪካውያን ብቻም ሳይሆን ለዓለምን ህዝብ ግራ ሆነው ተጉዘዋል፤ አሁንም በዚሁ ቀጥለዋል። ፕሬዚዳንቱ ዛሬም እንደ ትናንቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ የሚሰነዝሩት ዘለፋ የብዙዎች መነጋገሪያ እየሆነ ነው፡፡ ከአንደበታቸው የሚያፈልቁት ያልተጠበቀ ትችት ገሚሱን ፈገግ፣ ሌላውን አንጀት እያሳረረ ነው፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከእርሳቸው በፊት የነበሩትን ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የዘረጓቸውን ስርዓቶች፣ የገቧቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በማፍረስ እና የራሳቸውን መንገድ በመከተል አጀብ ማሰኘታቸውን ገፍተውበታል፡፡ ወደ ስልጣን እንደመጡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኦባማ በጤናው ዘርፍ ዜጎቻቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ የዘረጉትን ኦባማ ኬር አላስፈላጊነት በማወጅ አስነሱ፡፤ አሜሪካ ከኔቶ አባልነት ራሷን ታገላለች ሲሉም ተደመጡ፡፡ በሚያመነጩት የተቃርኖ ሃሳብ ከአገር ውስጥም ከውጭም ተቃውሞና ትችትን ማስተናገዳቸው ለእሳቸው ምንም ከመሆን አልዘለለም፡፡
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር የተፈራረሙትን ዓለም አቀፍ ስምምነት በፕሬዚዳንት ትራምፕ ውድቅ መሆኑ ብዙዎችን አነጋግሯል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ታዲያ በዚህ ብቻ የሚያቆሙ አልሆነም በዘመነ ኦባማ አገራቸው ከቻይና፣ ጀርመን፣ እንግሊዝ፣ፈረንሳይ ከኢራን ጋር የደረሱትን የኢራንን የኒውክሌር ማምረት ተግባር የማቆም መርሀ ግብር ስምምነት ላይ ውሃ ቸለሱበት፡፡ ይህም የሰሞኑ መነጋገሪያ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
አሁን በዶናልድ ትራምፕ ዘመን እንደሚጣስ የተነገረለት ዓለም ዓቀፍ ስምምነት ፤በሚያዝያ ወር
እ አ አ 2015 የተወሰነው። ኢራን የኒውክሌር መርሐ ግብሯን እንድታቋርጥ መስማማቷን ተከትሎ ፤ ለአገሪቱም በዓመት ከ110 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንዲሰጣትና የተጣለባት ማዕቀብ እንዲነሳ ከስምምነት የተደረሰ ነበር።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ዛሬ ላይ ደርሰው አሜሪካ በወቅቱ ያደረገችው ስምምነት ያልተገባ ነበር ሲሉ ወርፈውታል። ስምምነቱን "የማይረባ" እያሉ እስከመጥራት መድረሳቸው ፕሬዚዳንቱ በቀድሞው የፕሬዚዳንት ኦባማ መንገድ ላይ ያላቸውን ጥላቻ የሚያሳይ መሆኑን የሚናገሩ አሉ፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በአቋማቸው በመጽናት ከስምምነቱ አሜሪካ ራሷን የምታገል መሆኑን በአፅንዖት ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ኢራን አሁንም የኒውክሌር መሳሪያ እያመረተች መሆኑን በምክንያትነት ይጠቅሳሉ፡፡ ልማቱን በድብቅ ገፍታበታለች እያሉም ነው፡፡
ይህ የፕሬዚዳንት ትራምፕ አቋም እንደ ሁልግዜው ሁሉ ከውጪም ሆነ ከውስጥ አካላት የተቃውሞ ድምጾችን እያሰተናገደ ነው፡፡ በኢራን የኒውክሌር ጉዳይ ላይ የከረረ አቋም ከመያዛቸው ጋር የእስራኤል ፍላጎት ጎልቶ ተንፀባርቋል፡፡ እስራኤል በቅርቡ «ኢራን ከተግባሯ አልታቀበችም » በማለት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ አስታውቃለች፡፤ ይህንን የሚያረጋግጥ ባለ 55ሺ ገፅ ሰነድ በእጇ ማስገባቷን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔትንያሁ አስታውቀዋል፡፤ ይህ የእስራኤል መግለጫ ለአሜሪካ ተጨማሪ ግብዓትና ኃይል መሆኑ ነው የሚነገረው፡፤
ከሰባት ወራት በፊት የአገሪቱን የኑክሌር መርሃ ግብር በተመለከተ የቀረበላቸውን ስምምነት አልፈርምም ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ይባስ ብለውም እስካሁን ድረስ በኢራን ላይ ኢኮኖሚዋን የሚያሽመደምዱ ሁለት ማዕቀቦችን ጥለዋል፡፡ በኢራን ላይ የያዙትን አቋም ዛሬም አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ እርሳቸው በሃሳባቸው ጸንተው ቢጓዙም መንግሥታቸው በኢራን ጉዳይ ላይ እያራመደ ያለውን መንገድ ሰከን ብሎ እንዲመለከተው ከዓለም መንግሥታት፣ከአውሮፓ ኅብረት እና የአሜሪካ የቅርብ ወዳጅ ከሆኑት አገራት በኩል ተጠይቀዋል፣ተመክረዋል።
የፕሬዚዳንት ትራምፕን የደነደነና የገነገነ ልብ ለማፍረስ ከውጪና ከውጪ ሃሳባቸውን እንዲቀይሩ የሚሞግቱ ወገኖች ግን አላፈናፍን ብለዋቸዋል። ከጅምሩ ጀምሮ የዶናልድን ሃሳብ የሚሞግተው የእንግሊዝ መንግሥት አሁንም የትራምፕ አስተዳደር ከሃሳቡ ፈቀቅ እንዲል ግፊቱን እና የማግባባት ተግባሩን መቀጠሉን ቢቢሲ አስነብቧል። እስራኤል በኢራን ላይ የሰጠችውን መግለጫ ተከትሎ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ አገራቸው ከኢራን ጎን እንደምትቆም መናገራቸው ይታወሳል፡፤ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮንም የ2015 ስምምነት መከበር እንዳለበት በመጠቆም አሜሪካ ጉዳዩን ቆም ብላ እንድትመለከተው አሳስበዋል፡፡
ቢቢሲ ከትናንት በስቲያ እንዳስነበበው ፤የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በኢራን ኑክሌር ስምምነት የጋራ የድርጊት መርሐ ግብር ላይ አሜሪካ ከስምምነቱ እንዳትወጣ ለመደራደር ወደ ዋሽንግተን አቅንተዋል፡፡ ቦሪስ ከስፍራው የተገኙበት አጀንዳ አንድና አንድ ነበር፤ ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር በኢራን የኒውክሌር ጉዳይ ላይ በመወያየትና በመምከር ፕሬዚዳንቱ የያዙትን አቋም ማስለወጥ። በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በኢራን የኒውክሌር ጉዳይ ላይ የተደረሰውን ስምምነት የመጣስ አቋምን ለማስቀየር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተልዕኮ ተሰጥቷቸዋል፡፡
የትራምፕ አስተዳደር እአአ ግንቦት 12 ቀን 2018 ስምምነቱን የማንሳት እርምጃ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ቀነ ገደብ አስቀምጧል፡፡ የቦሪስ ጆንሰን ከስፍራው መገኘት ታዲያ ቀነ ገደቡ ከመድረሱ በፊት አቋም ለማስቀየር መሆኑን ዘጋርዲያን ፅፏል፡፡ «ዶናልድ ትራምፕ በጉዳዩ ላይ ጠንካራ ትችት እንዳላቸው እናውቃለን፤ ነገር ግን ለማስቀየር ወደኋላ አንልም»ዘገባው አመልክቷል፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የአቋም ለውጥ እንዲያደርጉ ከውጪና ከውስጥ ግፊቱ ጨምሯል፡፡
ራዲዮ ኒውዚላንድ በኢራን ጉዳይ ላይ ባወጣው ዘገባ የአሜሪካ መንግሥት ኢራን የኒውክሌር መሳሪያ የማብላላት ተግባሯን እንዳላቆመች አሁንም እየሞገተ መሆኑን ጽፏል። እስራኤል በጉዳዩ ላይ ምርመራ በማድረግ « ኢራቅ ከ 15 ዓመት በፊት የኒውክሌር መርሐ ግብሩን ታካሂድበት በነበረው ሞታባላድ በሚባል ስፍራ በሚስጥር የኒውክሌር የጦር መሳሪያ እያብላላች መሆኑን «የኢራን ሚስጥራዊ ሰነዶች» ያለቻቸውን መረጃዎች በመያዝ እየሞገተች እንደሆነ አመልክቷል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ‹‹በእስራኤል መንግሥት ይፋ የተደረገው ሰነድ፤እኤአ 2015 የኢራን የኑክሌር ትብብር ስምምነት ተግባራዊነት ውሸት መሆኑን የሚያሳይ ነው» ማለታቸውን ዘገባው ጠቅሷል። የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዋሽንግተን ቆይታቸው የአሜሪካን መንግሥትን አቋም ለማስቀየር የሚችል ውይይት ስለማድረጋቸው ጥርጣሬ መፍጠሩ ዘገባው አትቷል፡፡
ዘጋርዲያን ደግሞ የእስራኤልን መረጃ መሰረት በማድረግ ከድምዳሜ የደረሰውን የአሜሪካን መንግሥት ከአቋሙ ፈቀቅ ማለት እንዳለበት ኢራን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ጃቨድ ሻሪፍ በኩል አሳስባለች፡፡ «የቤንጃሚን ኔትንያሁ መንግሥት በምርመራ አገኘው የሚሉት መረጃ ከእኛ ተግባር የራቀና የሃሰት ነው።በእስራኤል የቀረበው ሰነድ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኒውክሌር ጉዳይ ተጠባባቂ በሆነው የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ቀደም ሲል ተዘጋጅተው የነበሩት ዶክመንቶችን በማሻሻል የቀረቡ ናቸው» ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መሞገታቸውን ዘገባው አስታውሷል። አሜሪካ አቋሟን እንድትቀይር እንግሊዝን የመሳሰሉ አገራት ግፊት እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆንሰን የአሜሪካን ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንሲና የአገሪቱ የጸጥታ ጉዳይ አማካሪውን ጆን ቦልተን እና በኮንግረሱን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አመራሮችን ያነጋግራሉ፡፡ በቆይታቸውም በፕሬዚዳንት ትራምፕ የተያዘው ከስምምነቱ የመውጣት አቋም ድጋፍ እንዲያጣ ማድረግ የሚያስችል ሥራ ሊሠሩ ይችላሉ የሚል ግምት ተይዟል፡፡
ሚስተር ጆንሰን « እንግሊዝ ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና የአውሮፓ አገሮች በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ባለው የላላ የጸጥታ ሃይል ዙሪያ መፍትሄ በማፈላለግ ረገድ አንድነትን ፈጥረው ተጉዘዋል። አገራቱ የጋራ አቋም በመያዝ መጓዝ የቻሉ እንደመሆናቸው በኢራን ጉዳይም የሚኖረን ድርድር በውጤት ለማጠናቀቅ የሚቻል ነው›› ማለታቸውን ዘጋርዲያን ዘግቧል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በኢራን ዙርያ የያዙት አቋም በእስራኤል ቢደገፍም ሌሎቹ አገራት አሜሪካ አቋሟን ልታስተካክል እንደሚገባ እየሞገቱ ነው፡፡ፕሬዚዳንቱ አቋማቸውን በመለወጥ በስምምነቱ ይቀጥሉ ይሆን? ወይስ ስምምነቱን በማቋረጥ በአቋማቸው ይገፋሉ? የሚለው የብዙዎች መልስ ያላገኘ ጥያቄ ነው፡፡

 ዳንኤል ዘነበ

Published in ዓለም አቀፍ

ሁሌም በአባራሪና ተባራሪ ተዋናዮች የሚደምቁ አደባባዮችና ጎዳናዎች በበርካታ ታዳሚዎች ይጎበኛሉ፡፡ አባራሪው ህግን ለማስከበር፤ተባራሪው ለዕለት ጉርሱ የሚሆነውን ገቢ ለማግኘት የያዘውን ለመሸጥ ይሯሯጣሉ፡፡ ታዳሚው ያሻውን ለመግዛት በትዕይንት መድረኩ ይገናኛሉ፡፡
በከፍተኛ ትርምስና ግርግር በተሞሉት አካባቢዎች በደንብ አስከባሪውና በተባራሪ ነጋዴው መካከል የሚስተዋለው የአባሮሽ ትንቅንቅ ዛሬም መፍትሔ አላገኘም፡፡ በእነዚህ ጎዳናዎችና አደባባዮች መገፈታተርና መጎነታተል፣ መጨቃጨቅና መነታረክ፤ ብቻ ብዙ ትዕይንቶች ይስተዋላሉ፡፡ በፒያሳ፣ ስድስት ኪሎ፣ መገናኛ፣ በሜክሲኮና በሌሎችም አካባቢዎች የጎዳና ላይ ንግዶች በበርካታ ታዳሚዎች ይጎበኛሉ፡፡ የሠራተኛ መውጫና መግቢያ ሰዓት ደግሞ ትዕይንቶቹ ሞቅ ብለው የሚስተዋሉባቸው ሠዓታት ናቸው፡፡
አሁን አሁን መንገደኛው የአባራሪና የተባራሪ ሁነቶችን መመልከት ብዙም አያስደንቀውም፡፡ ደንብ አስከባሪው ህጉን ለማስከበር ነጋዴዎቹን ያባርራል፤ዕቃዎችን ይነጥቃል፡፡ ተባራሪው ነጋዴ ከሸማች ጋር ተደራድሮ ዕቃውን ለመሸጥ በግማሽ ልብ ሆኖ ይጥራል፤ ዕቃው እንዳይወረስበት ከደንብ አስከባሪዎች ይጠነቀቃል፡፡
በየጎዳናው የማይሸጡ ሸቀጦች የሉም ማለት ይቻላል፡፡ አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ጣፋጭ ብስኩቶችና ከረሜላዎች፣ ብርቱኳንና ሙዝ፤ጎመንና ሰላጣ፤ የማዕድ ቤት ዕቃዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፤
የጎዳና ላይ ንግዶቹ እግረኛው ከመንገዱ ወጥቶ እንዲሄድ እያስገደዱ ነው፡፡ የትራፊክ ፍሰቱን በማጨናነቅ ረገድም አቻ የላቸውም፡፡ ከእግረኞች መንገድ አልፈው የአሸከርካሪዎችን መንገድ እየዘጉ ነው፡፡ በከተማዋ ውበት ላይ እያሳደሩት ያለው አሉታዊ ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡
ነጋዴዎቹ ንግድ ፈቃድ አውጥተው የማይሰሩ በመሆናቸው መንግስት ከታክስ ማግኘት የሚገባውን ከፍተኛ ገንዘብ ያስቀራሉ፡፡ ህጋዊ ፈቃድ አውጥቶ የሚነግደውን ነጋዴ ህልውና ይፈታተናሉ፡ ህገ ወጥነት እንዲስፋፋ ያደርጋሉ፡፡ በአብዛኛው ጥራት የጎደላቸውና የአገልግሎት ዘመናቸው ያለፈባቸው ምርቶች ለገበያ የሚቀርቡበት አጋጣሚ ከፍተኛ በመሆኑም የዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ ይጥላሉ፡፡ በዚህ ረገድ በተለይም የምግብ ሸቀጦች ከፍተኛ የጤና ስጋት መሆናቸው ነው የሚነገረው፡፡
የእነዚህ ሽቀጦች ከፍተኛው ምንጭ ኮንትሮባንድ እንደሆነ ነው የሚነገረው፡፡ አንዳንድ ትላልቅ የአልባሳትና ሸቀጣሸቀጥ አከፋፋይ ተቋማትና ቸርቻሪዎች ከመደብሮቻቸው አልነሳ ያላቸውንና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን ሸቀጦች በጐዳና ንግድ ላይ ለተሠማሩ ሕገወጥ ነጋዴዎች እንደሚያከፋፍሉ ይጠቀሳል፡፡ ይህን አካሄድ ህጋዊው ነጋዴ በሌላው መልኩ የጎዳና ንግዱን እያደፋፈረ የመሆኑ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ችግሩን ለማቃለልና ለማስወገድ ደንብ አስከባሪ አካላት ቢጥሩም በተጨባጭ የመጣ ውጤት የለም፡፡ ነጋዴዎቹ ደንብ አስከባሪዎቹን ሲመለከቱ የሚግባቡበት ቋንቋ አላቸው፡፡ ደንብ አስከባሪዎችን ቀድሞ የተመለከተ ለሌሎቹ ባልደረቦቹ ‹‹ተበላህ›› እያለ ይሮጣል፡፡ ይህኔ ሁሉም እግሬ አውጭኝ ይላሉ፡፡ ንብረታቸውን ላለማስነጠቅ ይደበቃሉ፣ ይሮጣሉ፡፡
የጎዳና ላይ ነጋዴዎች በተለያዩ አካባቢ እንዲሸጡ ቦታ ቢመቻችላቸውም ፍቃደኛ እንደማይሆኑ ይገለፃል፡፡ የጎዳና ንግዱ ከኪራይ ውጭ በመሸጥ ትርፋማ እንዲሆኑ ከማስቻሉም በላይ ብዙ ሸማችን ለማግኘት ይረዳቸዋል ይባላል፡፡ በዋጋ ላይ የሚፈጥሩት ቅናሽ በህጋዊ ነጋዴዎች ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ለመንግሥት ግብር አይከፍሉም፣ የቤት ኪራይና ሌሎች ወጪዎችን አያወጡም፡፡ ስለሆነም በቅናሽ ዋጋ በመሸጥ ተጠቃሚውን ይይዛሉ፡፡ ኅብረተሰቡም ጥራትና የአገልግሎት ዘመንን ከማየት ይልቅ በዋጋ መቀነስ ላይ በማተኮር በጐዳና ንግድ ይሳባል፤ ይማረካል፡፡
በ‹‹ተበላህ›› መድረክ ‹‹ወይ አንሳ ወይ ሃምሳ›› የሚል አባባል መኖሩ ይነገራል፡፡ ይህቺ አባባል አንዳንድ ደንብ አስከባሪዎች ከነጋዴዎቹ ጋር የሚግባቡባት የ‹‹እከክልኝ ልከክልህ›› የጥቅም ትስስር ነች ይባላል፡፡ ነጋዴው ላለመባረር ለደንብ አስከባሪው ሃምሳ ብር ይሰጣል፡፡ ለማዶቹ ደንብ አስከባሪዎች ሲሄዱ አዲሶች ሲመጡ የአባሮሹ ፍጥነት ይጨምራል፡፡ በጊዜ ሂደት መላመዱ ሲመጣ ‹‹እንጠቃቀም›› ትነግሳለች የሚሉ ወሬዎች ይሰማሉ፡፡ እናም ግርግሩ ለታይታ ብቻ ይሆናል የሚሉ አሉ፡፡
የጎዳና ላይ ንግዱ ከእኔ ብጤዎች ፣ ቆሎና ለውዝ የሚሸጡ ህፃናት፣ ሳምቡሳና ቺፕስ የሚጠብሱ፣ ድንች የሚቀቅሉ ፤ ሱቅ በደረቴዎቹ ‹‹ጀብሎዎች››፣ ሎተሪና መፋቂያ አዟሪዎች፣ ሶፍትና ሌሎች ሸቀጥ አዟሪዎች ጋር ተዳምሮ አካባቢውን መተንፈሻ ያሳጡታል፡፡ ዕቃ ሲረገጥ ግልምጫና ስድቡ መዓት ነው፡፡ መንገዱ የተፈቀደለት መንገደኛ መብቱን ከመገፈፉም በላይ የስድብ ውርጅብኝ ይወርድበታል፡፡
አሁን አሁን ደግሞ አምፖሎች፣ የመንጃ ፍቃድ መማሪያ መጽሐፍትና ሲዲዎች፣ኬክና ብስኩቶችን በተሽከርካሪ ጭኖ መሸጥ የተለመደ ሆኗል፡፡ እነዚህኞቹ ሱቅ ከፍተው ከሚሸጡት ዕኩል እንዲያውም ባይበልጥ በሚያስብል ደረጃ አቅም እያላቸው ወደዚህ መምጣታቸው ብዙዎችን ግራ ያጋባል፡፡ ምናልባትም ከግብርና ከሱቅ ኪራይ ነፃ ሆኖ በመሸጥ ብዙ ማትረፍን ዓላማቸው ስላደረጉ ሳይሆን አይቀርም፡፡
የጎዳና ላይ ንግድ የከተማዋ ቁልፍ ችግር ሆኖ ከከተማዋ ጋር ተጣብቆ ጉዞውን በመደበኛነት ቀጥሏል፡፡ አሁን ችግሩ እየሰፋ ሄዶ ከእለት ተዕለት እንቅስቃሴ ጋር ተዋህዶ መደበኛ የሥራና የኑሮ አካል ወደ መሆን ደርሷል፡፡ የጎዳና ላይ ንግድ አንዱ የዕድገት ማነቆ መሆኑ በተደጋጋሚ ቢነገርም መፍትሔ አልተበጀለትም፡፡ ችግሩን ለማስቆም የተለያዩ ስትራቴጂዎች ቢነደፉም በተግባር ያመጡት ለውጥ የለም፡፡ ‹‹ተደራጅተው እንዲሰሩ ይደረጋል፤ በህጋዊ የንግድ መስመር እንዲመሩ መመሪያ ተዘጋጅቷል››ቢባልም ውጤቱ ምንም ከመሆን አልዘለለም፡፡
ችግሩን ለመከላከል እየሰለጠኑ ወደ ሥራ የሚገቡት ደንብ አስከባሪዎችም ግርግር ከመፍጠር ያለፈ ውጤት አላመጡም፡፡ ደንብ አስከባሪዎች ለተወሰነ ጊዜ ታይተው ይጠፋሉ፡፡ ሲመጡም ለተወሰኑ ደቂቃዎች አባሮሹን ጀምረው ከመሄድ ያለፈ የሚያደርጉት ነገር የለም፡፡‹‹ለደንብ አስከባሪዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል›› በማለት የደንብ ማስከበር እንቅስቃሴውን ፋይዳ ቢስነት የሚናገሩም አሉ፡፡
ደንብ አስከባሪዎች በተለይም በተሽከርካሪ የሚነግዱትን ሲጠይቁ አይስተዋልም፡፡ በተሽከርካሪ መነገድ ህጋዊ ይመስል ዝም ብለው ያልፏቸዋል፡፡ ይህ ዝምታ የተሽከርካሪ ላይ ንግድ እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል፡፡ ምናልባትም እነዚህኞቹ ለአንዳንድ ደንብ አስከባሪዎች ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ሳይሆኑ እንዳልቀረ ጥርጣሬያቸውን የሚያስቀምጡ አልጠፉም፡፡
ይህ የጥርጣሬ ዕይታ ደምብ አስከባሪዎች የጎዳና ላይ ነጋዴዎችን ዕቃ ለመውረስ በማስፈራራት በእጃቸው እንዲሸጎጥላቸው ይጠቀሙበታል ከሚል እምነት የሚመነጭ ነው፡፡
ነጋዴዎቹም ይህንን ስለሚያውቁ ደምብ አስከባሪዎች ብቅ ሲሉ የሚቃጣባቸውን ጡጫ ለማስቀረት ጊዜያዊ ማስታገሻ የሆነውን ጉርሻ ያስጨብጣሉ፡፡ የጎዳና ላይ ንግድ ህዝቡንም አገርንም እየጎዳ በመስፋፋቱ ጎዳና ቀጥሏል፡፡
በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ20 ሺ ለሚበልጡ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ስልጠና መስጠቱን አስታውቋል፡፡ በዚህም ወደ መደበኛ የንግድ ሥርዓት እንዲገቡ ይደረጋል ነው የተባለው፡፡ ይህን ማድረግ ከተቻለ ውጤት መምጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ ሆኖም ግን አሁንም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ በተለይም ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ የማከናወኑ ጥረት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡
ከአገሪቱ አጠቃላይ ንግድ ከ40 እስከ 50 በመቶ የሚሆነው የሚከናወንባትን አዲስ አበባን ከጎዳና ንግድ ለመታደግ ብዙ መስራት ያስፈልጋል፡፡ የነጋዴዎቹ የዕረፍት ቀናት (ሰንደይ ማርኬት) እንዲሸጡ ግንዛቤ ማስጨበጥና መወያየት ተገቢነቱ አያጠያይቅም፡፡ መንገዶች ለታለመላቸው ዓላማ ብቻ እንዲውሉ ማድረግም ይገባል፡፡ ህዝቡን ከእንግልት፤አገርን ከጉዳት ለመከላከል የጋራ ጥረቱ ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል ግድ ይላል፡፡ የ‹‹ተበላህ›› ሜዳ ሩጫውን ለማስቆም አፋጣኝ የመፍትሔ እርምጃ ያሻዋል፡፡

ሠላም ዘአማን

Published in አጀንዳ

መንግስት በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የአገር ውስጥ ስኳር ፍላጎትን በማረጋገጥ ከዘርፉ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ትልቅ ግብ አስቀምጦ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል፡፡ በዚህም መሰረት በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ ወደ ምርት የሚገቡ 10 የስኳር ፋብሪካዎችን ግንባታ ለማከናወን ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡
ስኳር ፋብሪካዎቹ በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ 2 ነጥብ 25 ሚሊዮን ቶን ስኳር ለማምረት፣ ከሚመረተው ምርት ደግሞ አንድ ነጥብ 246 ሚሊዮን ቶን ስኳር ለዓለም ገበያ በማቅረብ 661 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር የማግኘት ግብም ተቀምጦላቸዋል፡፡ ለ200ሺ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠርም የሥራ አጡን ቁጥር የመቀነስ ተስፋም ተጥሎባቸዋል፡፡
ይህ በመንግስት የተያዘው እቅድ ታዲያ በተያዘለት ጊዜ ዕውን ሆኖ በተግባር ለመታየት ተስኖት ወደ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለመዛወር ተገዷል፡፡ በአምስት ዓመት በተግባር ለመታየት የተነደፈው ዕቅድ በሰባት ዓመት ተኩልም ሊሳካ አልቻለም፡፡ በዚህም አገሪቱ ለተጨማሪ ወጪ ተዳርጋለች፡፡ ስኳርን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት የታሰበው ግብ ባለመሳካቱ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ ለመግዛት ተገዳለች፡፡
በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨረሻ ስኳር ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ግብ የያዘችው ኢትዮጵያ፣በ 2010 በጀት ዓመት እስከ አሁን ድረስ ብቻ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ገዝታለች፡፡ ተጨማሪ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ለመግዛትም በግዥ ሂደት ላይ ነች። ይህም ቢሆን የህዝቡን ፍላጎት የሚያረካ አልሆነም፡፡ በየጊዜው ከፍተኛ የስኳር እጥረት እየተከሰተ ህዝቡ ቅሬታውን እያሰማ ነው፡፡ ከሸማቾች ማህበራት ስኳርን ለመግዛት የሚደረገው ሰልፍ አስደንጋጭ ነው፡፡ ፕሮጀክቶቹ በመጓተታቸው በህዝብና በመንግስት መካከል መተማመን እንዳይኖርም የራሳቸውን ድርሻ አበርክተዋል፡፡
ፋብሪካዎቹ በተያዘላቸው ጊዜ ላለመጠናቀቃቸው የተለያዩ ምክንያች ቢሰነዘሩም የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓቱ መላላት በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ ይህ ደግሞ ኃላፊነትን በአግባቡ ካለመወጣት ጋር ይያያዛል፡፡ ፕሮጀክቶቹን በበላይነት የሚቆጣጠረው አካል ጠንካራ የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓት ዘርግቶ ከመራመድ አንፃር ብዙ ድክመቶችና ክፍተቶች አሉበት፡፡ ሥራ ተቋራጮችና አማካሪዎች በየቀኑ የሥራውን አፈፃፀም እንዲልኩለት ከማድረግ ይልቅ ችግር ተፈጠረ ሲባል ወደ ፕሮጀክቶቹ ሲያቀና ይስተዋላል፡፡
ይህ ደግሞ ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ የሚደረግ ሩጫ በመሆኑ ውጤቱ ብዙም አይደለም፡፡ ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሔ በማበጀት ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ከማድረግ ይልቅ ጊዜያዊ መፍትሔ ሰጥቶ የማስቀጠል አካሄድን መከተልም የተለመደ ሆኗል፡፡ ችግር ያለበት አካል በገባው ውል መሰረት ሲጠየቅ አይስተዋልም፡፡ ለጥፋቱም ካሳ እንዲከፍል አይደረግም፡፡ የፕሮጀክቶቹ ባለቤት የሚጠበቅበትን ሳይወጣ ሲቀር የበላይ ተቆጣጣሪውም የሚወስደው እርምጃ አለመኖሩ ችግሩ እየተከማቸ እንዲሄድ አድርጓል፡፡
በተለይም የህዝብ እንደራሴ የሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሚቀርብለት ሪፖርት ባለፈ ፕሮጀክቶቹ ያሉበት ቦታ ድረስ በየወቅቱ በመሄድ የመስክ ምልከታ ማድረግ ቢጠበቅበትም በዚህ በኩል ከፍተት መኖሩ ግልፅ ነው፡፡ የስኳር ፋብሪካዎች መዘግየትና ችግራቸው ተቆልሎ ግንባታዎችን እስከማቆም የሚደርስ እርምጃ መወሰዱ በየጊዜው የሚደረግ ክትትል አለመኖሩን በግልፅ ያሳያል፡፡
የመጨረሻው የውድቀት ምዕራፍ ላይ ሲደርስ ፕሮጀክቶችን ከአንድ ሥራ ተቋራጭ ነጥቆ ለሌላው መስጠት መፍትሔ አይሆንም፡፡ ዋናው ጉዳይ ጠንካራ የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡ በዚህም የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በአግባቡ ያልተወጣ ሥራ ተቋራጭ፣አማካሪና አሠሪ ድርጅት በህግ አግባብ ሊጠየቁ ይገባል፡፡
ከላይ ሆኖ ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርገው አካልም ችግሮች ከመከማቸታቸው በፊት ከሥር ከሥር መፍትሔ እንዲያገኙ መስራትና መከታተል ይኖርበታል፡፡ ከሪፖርት መረጃ በመውጣት መረጃና ማስረጃን ከምንጩ የማግኘት ባህል ሊዳብርና ሊጠናከር ይገባል፡፡ ህዝብና አገርን ይጠቅማሉ ተብለው ከፍተኛ የአገር ሀብት ወጭ የተደረገባቸው ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጥራት ደረጃ፣ገንዘብና ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ሁሉም የቤት ሥራውን በአግባቡ መወጣት ይጠበቅበታል፡፡ ኃላፊነትን ባለመወጣት በሚደርሱ ጉድለቶች አገርና ህዝብ መጎዳት የለባቸውም፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

በከተሞች የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ መጓተት አገሪቱ እየተጎዳች መሆኑን የውኃ ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ ባለመጠናቀቃቸው የመጠጥ ውሃ አቅርቦቱን በማስተጓጎል ዜጎችን ለውሃ ጥም፤ አገሪቱን ለብድር ጫና ዳርገዋል፡፡

ጽህፈት ቤቱ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶችና መንግሥታት ከሚያገኘው ብድርና ዕርዳታ፤ እንዲሁም በመንግሥት ከሚመደብ በጀት ለከተሞች የመጠጥ ውሃ ግንባታ ብድር ቢሰጥም በፕሮጀክቶቹ መጓተት ብድሩ በወቅቱ እየተመለሰ አይደለም፡፡ ይህም ገንዘቡን ለሌሎች ከተሞች በመስጠት የመጠጥ ውሃ ግንባታ እንዲያከናውኑ የሚደረገውን ጥረት አስተጓጉሎታል፡፡ ለዜጎች የመጠጥ ውሃ ለማቅረብ ለተያዘው ዕቅድም ዕንቅፋት ሆኗል፡፡
ባለፉት 16 ዓመታት ለ89 የውሃ ፕሮጀክቶች 9 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ብድር መሰጠቱን የፅህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዋና ዋኬ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ 27ቱ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ ቀሪዎቹ በተለያየ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
የአብዛኞቹ ፕሮጀክቶች ገንዘብ መንግስት ከውጭ በብድርና እርዳታ የሚያገኛቸው ሲሆን ብደሩ የሚከፈለበት ጊዜም ከአበዳሪዎቹ ጋር በውል ታስሯል፡፡ ጽህፈት ቤቱም ለከተማ አስተዳደሮች የጊዜ ውል አስሮ ብድሩን ቢሰጥም ከተሞቹ በፕሮጀክቶቹ መጓተት ምክንያት በገቡት ውል መሰረት ገንዘቡን እየመለሱ አለመሆናቸውን ነው ፅህፈት ቤቱ ያስታወቀው፡፡
የፕሮጀክቶቹ መዘግየት ለዜጎች የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማዳረስ በሚደረገው ጥረት ላይ እንቅፋት መሆኑን አቶ ዋና ይገልፃሉ፡፡ የመጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በማስተጓጎል ውሃ መጠጣት ያለባቸውን ዜጎች ለውሃ ጥም ዳርጓል ይላሉ፡፡ ከፅህፈት ቤቱ ብድር የወሰዱ ከተሞች የውሃ ፕሮጀክቶችን በወቅቱ ገንብተው ብድሩን ባለመመለሳቸው ሌሎች ከተሞች ብድር ወስደው ግንባታ እንዳያከናውኑ ማድረጉን ያስረዳሉ፡፡
የአርባምንጭ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የአካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬከተር ዶክተር ባሻህ ሞገሴ፤ በውሃ ፍለጋ፣ ዲዛይን፣ ግንባታና ከግንባታም በኋላ ባለው ጥገና የተቀናጀና የጋራ ተጠያቂነት ስርዓት ባለመዘርጋቱ ምክንያት በሚፈጠር የፕሮጀክቶች መዘግየት መንግሥት ለተጨማሪ ወጭ፤ ህዝቡ ለመጠጥ ውሃ እጥረት እየተዳረጉ ነው ብለዋል፡፡
ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ከህዝብ ቁጥር ጋር የሚጣጣም የውሃ ፕሮጀክት ሳይነደፍ፣ ሳይንሳዊ መሳሪያዎች ጥቅም ላይ ሳይውሉ፣ በአካባቢው ያለውን የአየር ንብረት ተጽዕኖ እና ማህበራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ሳይገባ በሚከናወን ሥራ የሚከሰተው የፕሮጀክቶች መዘግየት የመጠጥ ውሃ ተደራሽነቱን እየተፈታተነው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ጽህፈት ቤቱ የዘጠኝ ወር ሪፖርቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሀብትና አካባቢ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ ጀምበርነሽ ክንፈ፤ በመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች መዘግየት ህዝብና አገር ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአርሲ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ካሳሁን ዱባለ፤ ብድርን ለታለመለት ዓለማ አውሎ በአግባቡ አለመመለስ አገርና ህዝብን እንደሚጎዳ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ለብድር ወለድና ቅጣት የሚከፈለው ገንዘብ የአገሪቱን ዕድገት ያቀጭጫል። ዓለም አቀፍ ማዕቀብ በአገሪቱ ላይ ሊያስጥል ይችላል›› ያሉት ዶክተር ካሳሁን በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ያለባት ብድር 30 ቢሊዮን ዶላር እንደሚጠጋ መረጃዎች እንደሚያመላክቱ አስረድተዋል፡፡ እናም በብድር የሚመጣውን ገንዘብ በአግባቡ በሥራ ላይ በማዋል መመለስ ካልተቻለ አገርና ህዝብ በዕዳ ጫና ችግር ውስጥ ይወድቃሉ፣ መጪውን ትውልድ ባለ ዕዳ ያደርጋል ይላሉ፡፡
በሀገሪቱ በከተማና በገጠር የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን 67 በመቶ መድረሱን ከውሃ ፣መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡ ይህን ሽፋን በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ወደ 80 በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል፡፡ ዓመታዊ አማካይ የህዝብ ዕድገት ሦስት ነጥብ ስምንት በመቶ ከሆነው የኢትዮጵያ ከተሞች ጋር የሚመጣጠን የውሃ መሠረተ ልማት አለመኖሩን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ባለፈው ዓመት ከዓለም ባንክ ከ20 እስከ 40 ዓመታት ውስጥ የሚከፈል የ450 ሚሊዮን ዶላር ብድር ተገኝቷል። በተያዘው በጀት ዓመት መጋቢት ወርም በኢትዮጵያ ከተሞች የአስተዳደር አካላትን አቅም ለማሳደግ፣ መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት ከዓለም ባንክ የ600 ሚሊዮን ዶላር የብድርና ድጋፍ ስምምነት ተደርጓል። በተለያዩ ጊዜያትም በሁለትዮሽና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የተለያዩ የብድርና የዕርዳታ ስምምነቶች መደረጋቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የውሃ ፕሮጀክቶች መዘግየት ዜጎች የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ያደርጋሉ፡፡ ዜጎችን ለውሃ ወለድና ተያያዥ በሽታዎች ይዳርጋሉ፡፡ የከተሞችን ዕድገት ያቀጭጫሉ፤ የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎችን ይፈጥራሉ፡፡ አገሪቱ ብድሯን በወቅቱ እንዳትከፍል በማድረግ ለወለድ፣ ለቅጣትና ተደራራቢ የዕዳ ጫና ይዳርጋሉ፡፡ ከአበዳሪዎች የሚገኘው ብድር እንዲቀንስ ያደርጋሉ፡፡ መጭው ትውልድ የከፍተኛ ብድር ዕዳ ከፋይ ይሆናል፤ የአገሪቱን ዕድገት ያዳክማል፡፡ 

 

ዜና ትንታኔ
አጎናፍር ገዛኸኝ

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።